One cannot solve the monetary crisis of a given country by a neo-liberal economic policy
አንድን የኒዎ–ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን የሚያራምድ በሌላ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ባለው በመተካት የኢትዮጵያን የሞኔተሪ ወይም የገንዘብ ችግር መፍታት አይቻልም!
ኢዮብ ተካልኝም ሆነ ማሞ ምህረቱ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ ተቀጣሪዎች ናቸው!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
መስከረም 21፣ 2018 (October 1, 2025)
መግቢያ
በመጀመሪያ ደረጃ፣ እኛ ኢትዮጵያኖች ስለኢኮኖሚ በምናወራበት ጊዜ ስለምን እንደምናወራ በፍጹም የምናውቅ አይመስለኝም። በሁለተኛ ደረጃ፣ በተራ የሸቀጣ ሸቀጥ የገበያ ኢኮኖሚና በተወሳሰበውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ በሚደገፈው የካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርዓት መሀከል ያለውን ልዩነት በፍጹም አናውቅም። በሶስተኛ ደረጃ፣ ቢያንስ ባለፉት መቶ ዐመታት በምዕራብ አውሮፓ የሰፈነውንና፣ በተለይም ባለፉት ሰማንያ ዐመታት የዓለምን ህዝብ የሚያሽከረክረውንና የብዙ ቢሊዮን ህዝቦችን ህይወት የሚደነግገው የካፒታሊስት ኢኮኖሚ የተጓዘበትን ጠመዝማዛ መንገድ በጥብቅ የተከታተልን ወይም ያጠናን አይመስልም። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬ የሚታየውና የብዙ ቢሊዮን ህዝቦችን ህይወት የሚደነግገው የካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርዓት ከመመስረቱ በፊት የፊዩዳሉ ኢኮኖሚ ወይም ስርዓትና ርዕዮተ-ዓለሙ በፍልስፍና፣ በሳይንስ፣ እንዲሁም ቀስ በቀስ እየዳበረ በመጣው ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ መገርሰስ እንዳለባቸው በፍጹም ጥናት አላደረግንም። በአራተኛ ደረጃ፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በዛሬው መልክ ከመዳበሩ በፊት ከተማዎችና መንደሮች እንደተመሰረቱ፣ የዕደ-ጥበብ ሙያ እንደዳበረና፣ የንግድ ልውውጥም እንደተስፋፋ በፍጹም ግንዛቤ የለንም። በአምስተኛ ደረጃ፣ ተበታትነው የሚገኙ ህዝቦችንና ተሰበጣጥረው የሚገኙ ከተማዎችን ለማገናኘትና በንግድ አማካይነት ለማስተሳሰር የግዴታ መንገዶች፣ የካናል ሲይስተሞችና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በእንፋሎት የሚነዳ ባቡር እነደተነጠፉና፣ እነዚህ ሁሉ በመተሳሰር ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት እንደጣሉ ምንም ዐይነት ግንዛቤ የለንም። በስድስተኛ ደረጃ፣ ንግድን ለማስፋፋት ሲባልና የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮችን ለማስተሳሰር ገንዘብ የሚባለው ነገር በመጀመሪያ በወርቅና በብር ይገለጽ የነበረው(Coin Money) በወርቅ በሚደገፍ የወረቀት ገንዘብ እንደተተካና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የወረቀት ገንዘብ ከወርቅ በመነጠልና በመንግስት ድጋፍና ማረጋገጫ ህጋዊ የመገበያያ ገንዘብ እንደሆነ በፍጹም ግንዛቤ የለንም። በሰባተኛ ደረጃ፣ እነዚህ ሁሉ በመደማመርና በከፍተኛ ደረጃ ህዝብን በማፈናቀልና የጥሬ-ሀብትን በመዝረፍ፣ እንዲሁም የአፍሪካን ዕድገት በማጨናገፍና ሀብቷን በመዝረፍ ካፒታሊዝም እንዴት እንደተገነባ በፍጹም ለመመራመር አንቃጣም። አብዛኛዎቻንን በተለይም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሰለጠን የሚመስለን በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት አማካይነት መሰረት፣ ይህም የኢኮኖሚስ ትምህርት ኒዎ-ክላሲካል በመባል ይታወቃል፤ በዚህ አማካይነት የገበያ ኢኮኖሚ እንደተገነባ ነው የሚመስለን። ስለሆነም በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ሁሉም በእኩለነት የሚሳተፉበትና፣ የየዕቃዎችም ዋጋ በአቅራቢና በጠያቂ ህግ ብለው በሚጠሩት እንደሚደነገግ ነው የሚመስለን። በስምንተኛ ደረጃ፣ ሁላችንም በገበያ ኢኮኖሚ የሰለጠን ስለሆን በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ የመንግስታት ሚናን በፍጹም አንገነዘብም። ዘጠነኛ፣ ስለሆነም በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች እንደፈለቁና የሚደረጉትም ክርክሮች በመንግስታት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር እንደቻሉ በፍጹም ግንዛቤ የለንም። አስረኛ፣ በኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ውስጥ የፍዚዮክራቲክ የኢኮኖሚ ቲዊሪ፣ የመርከንታሊዝም የኢኮኖሚ ቲዎሪ፣ በእነ አዳም ስሚዝና ሪካርዶ እንዲሁም በሌሎች የእንግሊዝ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የተጠናውና የተጻፈው የኢኮኖሚ ቲዎሪ፣ የማርክሲዝም የኢኮኖሚ ቲዎሪ፣ ማርክሲዝምን በመቃወም የዳበረው የኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ፣ ቀጥሎም በእነ ሹምፔተርና በቬበሊን የሚወከለው ኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስ፣ የኬይንስ ኢኮኖሚክስና ከ1930ዎች አጋማሽ ላይ ደግሞ እየዳበረ የመጣው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በእነዚህ የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች መሀከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ በፍጹም ግንዛቤ የለንም። በተለይም የኒዎ-ክላሲካል፣ የኒዎ-ሊበራልና የኬይንስ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ካፒታሊዝም ከታች ወደላይ፣ ወይም ከዝቅተኛ ደረጃ(Simple Commodity Production) ወደ ከፍተኛ ደረጃ፣ ማለትም በኦሊጎፖሊዝና በሞኖፖሊ ካፒታሊዝም የሚገለፀው እንዴት ደረጃ በደረጃ እንዳደገና፣ በባንኮችና በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለውን መተሳሰር በፍጽም አይተነትኑም። በዚህም መሰረት የካፒታልዝምን ዕድገት ከዝቅተኛ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ስርዓት ባለው መልክና በጥልቀት የሚተነትነው በማርክስ የተጻፉት ዳስ ካፒታል ወይም ካፒታል በመባል የሚታወቀው በሶስት ቅጾች የተጻፉት መጽሀፎች ብቻ ናቸው። የሚያሳዝነው ነገር ግን አልፎ አልፎና በልዩ ኮርስ ካልሆነ በስተቀር የማርክሲዝም የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና ትንተና በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደ ቋሚ ትምህር አይሰጥም። በእነ ዕምነት የማርክሲዝምን የኢኮኖሚክስ ስራዎች በተከታታይ ያላነበበና ያላጠና ራሱን ኢኮኖሚስት ነኝ እያለ ሊጠራ በፍጹም አይችልም። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች በአንድ አገር ውስጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎች ሆነው በሚሾሙበት ጊዜ አንድን አገር በተሟላ ወይም ሁለ-ገብ በሆነ መልክ የመገንባት ኃይልና ችሎታ የላቸውም። ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚመጡትን ፖሊሲ የሚባሉ ዕቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ አንድን አገርና ህብረተሰብ ያዘበራርቃሉ። ስለሆነም ማንኛውም ስለ አገሬ ያገባኛል የሚል ሰው የግዴታ ስለኢኮኖሚ የዕድገት ታሪክ፣ የልዩ ልዩ አስተሳሰቦች መፍለቅና በየጊዜው የተደረገውን ክርክር፣ እንዲሁም ካፒታሊዝም ከላይ ወደታች እንዴት ደረጃ በደረጃ እንዳደገ መረዳትና መጻፍ አለበት። በደንብ ተገንዝቦም ማስተማር አለበት። አገሩን ከጥፋትና የወንበዴዎች መጨፈሪያ እንዳትሆን ማድረግ መቻል አለበት። የምሁር ነኝ ባይ ዋና ተግባሩም ይህ ነው። ማስተማርና ለደሃ ህዝብ ጠበቃ በመሆን የብርሃኑን መንገድ ማሳየት።
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማ!
የአንድ አገር ኢኮኖሚ ፖሊሲ የዓለም አቀፍ ተቋም ነኝ በሚሉና በሌላ ህብረተሰብና የኢኮኖሚ ስርዓት ባደጉ የሚታቀድ ወይም የሚወጣ ሳይሆን በአንድ አገር ምሁር ወይም ምሁራን አማካይነትየሚተገበር መሆን አለበት። የሚወጣውም ወይም የሚታቀደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድን አገር በተሟላ መልክ ለመገንባትና አንድን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ለማላቀቅና እንደ ሰው እንዲኖር ለማድረግ ብቻ ነው። የኢኮኖሚ ፖሊሲው ከመውጣቱም በፊት የህብረተሰቡን አወቃቀር፣ የተለያዩ ተቋማት መኖራቸውና አለመኖራቸውን፣ በተጨማሪም የአመራረት ስልትና ሰፊውን ህዝብ የሚመግበው ኢኮኖሚ መሰረቱ ወይም ስልተምርቱ ምን እንደሆነ መመርመር አለበት። ሰለሆነም በአንድ አገር ውስጥ በምሁራን አማካይነት የሚወጣ፣ የሚጻፍና የሚታቀድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንም ዐይነት ሰፊውን ህዝብ የማያፈናቅል፣ ያለውን ሀብት እንዲነጠቅ የማያደርግ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ ሀብቶችም ዝም ብለው እንዲቸረቸሩ የማያደርግ መሆን አለበት። ስለሆነም የአንድ አገር የኢኮኖሚ ፖሊስ በምንም ዐይነት የውጭ ኤስክፐርቶችን ነኝ በሚሉ፣ በተለይም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ(World Bank) የሚታቀድ መሆን የለበትም። እነዚህ ድርጅቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኤክስፐርት ነን በማለት መንግስታትን የሚያታልሉ በሙሉ የህብረተሰብ ታሪክ ዕውቀት የሌላቸው፣ በፍልስፍናና በሶስዮሎጂ ያልሰለጠኑ፣ በታሪክ ውስጥ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች እንደነበሩና፣ በዛሬው ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት የየአገሮችን ሀብት የሚያስቸበችብና ከሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ ወደ ድህነት የሚጥለውና በየአገሮች ውስጥ የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ የሚያስፋፋውን የማይገነዘቡና ለመገንዘብም የማይፈልጉ ናቸው። የዓለም አቀፍ ተቋማት የሚባሉትና በኢኮኖሚ ኤክስፐርትነት ስም የሚያወናብዱት በሙሉ ዋና ዓለማቸው ለፋይናንስ ካፒታል መስራትና ሀብትን ከሶስተኛው ዓለም አገሮች ወደ ካፒታሊስት አገሮች የሚተላለፍበትን ልዩ ልዩ መንገዶች ማመቻቸት ነው። አንደኛውና ዋና መሳሪያም አገሮችን የብድር ወጥመድ ውስጥ በመክተት መፈናፈኛ እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው።
ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የሚነደፈው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በራስ ጥረትና በአገር ውስጥ ሀብት አገርን ከታች ወደ ላይ በመገንባት ሰፊውን ህዝብ ከኋላ-ቀርነትና ከድህነት ማላቀቅ ነው። የአንድ አገር ኢኮኖሚና ህዝብን ከድህነት ማላቀቅ በዶላርና ከውጭ በሚመጣ “ዕርዳታ” በፍጹም መገንባት አይቻልም። በተለይም የኢኮኖሚክስ ቲዎሪን ከፍልስፍናና ከታሪክ ጋር በማገናኘት የጀርመንን ኢኮኖሚ ፖሊሲ የቀየሱና በእነቢስማርክ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደሩ እንደነ ፍሪድሪሽ ሊስት፣ ሮሽ፣ ሽሞለና ማክስ ቬበር፣ በኋላ ላይ ደግሞ ሃይንሪሽ ፔሽ የሚባሉት ታላላቅ መምህራን የሚያስተምሩን የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዋናው መሰረት ማኑፋክቸሪንግ ሲሆን፣ የጠቅላላው የኢኮኖሚ ፖሊሲም ዋና ዓላማ የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ነው። በተለይም የብሄራዊ ኢኮኖሚ መሰረተ-ሃሳቦች ወይም መማሪያ በማለት የጻፈው ሃይንሪሽ ፔሽ የሚባለው ታላቅ የኢኮኖሚስት መምህር የሚያስተምረን ቁም ነገር የኢኮኖሚ ዋናና ተቀዳሚ ዓላማ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) ማሟላት ነው። የእነዚህ ምሁራንም ዋናና የመጨረሻ መጨረሻ ዓላማ አንድን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በማላቀቅ ጠንካራ ብሄራዊ´ኢኮኖሚ በመገንባት(National Economy)አገርን ማስከበር ነው። በፍሪድሪሽ ሊስት ዕምነትና ትምህርት አንድ አገር ከውስጥ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ከተለያዩ መስኮች ጋር የተሳሰረ ኢኮኖሚ ከሌላት በቀላሉ በውጭ ኃይሎች ትጠቃለችች፣ ብሄራዊ ነፃነቷም ይገፈፋል ነው የሚለን።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተው መመሪያ፣ በመሰረቱ ፖሊሲ ያልሆነ በአገራችንና በሌሎችም አገሮች እንደተረጋገጠው የአንድን አገር ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በፍጹም የሚያላቅቅ አይደለም። እንዲያውም ለዝንተ-ዓለም በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚያደርግና የአንድን አገር የጥሬ-ሀብት የሚያስበዝብዝና ወደ ውጭ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው። በዚያውም አዳዲስ ያሸበርቁ ግለሰቦችንና የውጭ አገልጋይ የሆኑ በመመልመልና ታዛዥ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋሺዝምን ማስፋፋት ነው። ባለፉት አርባ ዓመታት እንደተረጋገጠው የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የእነ ዓለም ባንክ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሆኑባቸው ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮችና በደቡብ አሜሪካ ያለው ሃቅ የሚነግረን እጅግ የተወሳሰበ የፋሺዥም ስርዓት እንደተስፋፋ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ በሙሉ ከፍተኛ የውንብድና ስርዓት ሊስፋፋና፣ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍልም የተለያዩ የዕፅ ሱሶች ሰለባ በመሆን ማንነቱም እንዲስት ለመደረግ በቅቷል። በተለይም እንደነ ሜክሲኮ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ በድረግ ካርቴሎችና በመንግስት መኪናዎች መሀከል መተሳሰር ስለተፈጠረ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ደፋ ቀን የሚሉ የየክልልና የከተማ አስተዳዳሪዎች በጠራራ ፀሀይ ላይ ይገደላሉ። በአጭሩ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የረቀቀ የንዑስ ከበርቴውን ፋሺዝም ከማስፋፋት አልፎ አንድን አገር ታሪክ መስሪያና መኖሪያ እንዳይሆን ያደርጋል። የሚያሳዘነው ነገር በአገራችን ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚስት ነን እያሉ ራሳቸውን የሚያሞግሱና ከሰላሳ ዓመታት በላይ በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩና የሚሰሩትም ይህንን የጥፋትና የውንብድና መሰረት የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊስ ነው የሚያራምዱት።
የአንድ አገር ኢኮኖሚ በምርት ክንዋኔ የሚገለጽና የኢኮኖሚ መሰረትም ምርት ብቻ ነው!
በኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ እንደተረገጋጠውና ሎጂኩም እንደሚነግረን ምርትና የምርት ክንዋኔ ከመኖራቸው በፊት በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ ገንዘብ በፍጹም አልነበረም። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አካባቢና በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ የዕደ-ጥበብ ስራዎችና የእርሻ ምርት ከመመረታቸውና ወደ ገበያ ላይ ወጥተው ከመሸጣቸው በፊት ገንዘብ የሚባለው ነገር በፍጹም አልነበርም። ይህም ማለት የስራ-ክፍፍል ሲዳብርና ገበያ የሚባለውም ነገር ሲፈጠርና፣ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ሰዎችና አቅራቢ ነጋዴዎች ገበያ ላይ አውጥተው ለመሸጥ ያመቻቸው ዘንድ፣ በመጀመሪያ ወቅት አንድ ለጥቅም የሚውል ለምሳሌ አሞሌ ጨው ወይም ከብረትና ከቀንድ ከብት የተሰራ እንደገንዘብ ያገለግሎ ነበር። የኋላ ኋላ ላይ ይህ ሁኔታ ለንግድ ልውውጥ አስቸጋሪ ስለነበር ከመዳብ፣ ከብርና ከወርቅ የቀለጡና የየመንግስታት ስዕል ያለባቸው ሳንቲሞች መገበያያ መሳሪዎች በመሆን የንግድን ሂደትና መዳበር ሊያስፋፉ ችለዋል። በሌላ አነጋገር፣ በዛሬው ወቅት ተገልብጦ እንደሚታየውና ወደ ዕምነትም እንደተወሰደው ሳይሆን የአንድ አገር ህዝብ ዋናው ችግር ምርትን በብዛትና በልዩ ልዩ መልክ በማምረት ለገበያ ወይም ደግሞ ከፍሎ ለመግዛት ለሚችለው ማቅረብ ነው። አሁንም በሌላ አነጋገር፣ የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊና መሰረታዊ ችግር የአንድን አገር ገንዘብ ከሌላው ጋር ሲነፃፀር፣ አብዛኛውን ጊዜ ከዶላር ጋር ሲነፃጸር ዝቅ በማድረግ የሚፈታ ሳይሆን፣ ወይም ደግሞ በሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት የሚፈታ ሳይሆን በመጀመሪያ ደረጃ የመንግስትን አውቃቀር ሁኔታ፣ የፖለቲካውንና ጠቅላላውን የአመራረት ስልት ሁኔታ በመመርመር ብቻ የሚፈታ ነው። ከዚህም ባሻገር የአንድ አገር ኢኮኖሚ ችግር ከዕውቀት አለመስፋፋት፣ ከተማዎችና መንደሮች በስርዓት ካለመገንባት፣ የመመላለሻ መንገዶች በስዓርትና ሰፊውን ህዝብ በሚጠቅምና በማይጎዳ መልክ ካለመኖር ጋርና፣ የተቀላጠፉና ህዝባዊ ባህርይ ሊኖራቸው የሚችል ተቋማት አለመኖር ጋር የሚያያዝ በመሆኑ እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች በሙሉ ከታች ወደላይ እርጋኒካሊ ወይም በመተሳሰር ቀስ በቀስ፣ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ሊፈቱ ሲችሉ የኢኮኖሚው ችግርም ሊፈታ ይችላል። እንደሚታወቀው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በአየር ላይ ሳይሆን በጊዜና በቦታ(Space& Time) የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን በዚህ መልክ የሚያስቡ ሰዎች በአንድ ላይ በመስራት ሲያጠኑና ሲያቅዱ ብቻ የአንድ አገርም ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊፈታ ይችላል። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ የሚታቀድና በተግባር ላይ የሚውል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሌሎች ነገሮች ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ መጠን፣ የከተማ ዕቅድ አውጭዎች፣ ሶስይሎጂስቶች፣ የህሊና ሳይንስ አዋቂዎችና፣ በተለይም የህብረተሰብና የታሪክ ግንዛቤ ያላቸው ኢኮኖሚስቶች አንድ ላይ በመሆን በመመካከርና ሁለ-ገብ ዕቅድ በማውጣት ብቻ ነው የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር መፍታት የሚቻለው። ስለሆነም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ያላቸውና የውጭ ኃይሎች ተወካዮች የሆኑና የአገርን ሀብት የሚያዘርፉና ሰፊውንም ህዝብ ወደ ድህነት አሽቀንጥረው የሚጥሉ ግለሰቦች በማንኛውም የፖሊሲ ነክ ነገሮች ላይ መሰማራት የለባቸውም። ከዚህ ቀደም የዓለም አቀፍ የገንዘብና የዓለም ባንክ፣ እንዲሁም የዎል ስትሪት ተላላኪዎች በመሆን ህዝባችንን ወደድህነት የጣሉና ሀብትም ያዘረፉ በሙሉ አገር ቤት ውስጥ ካሉ በሰሩት የአገር ክህደት ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ሲገባቸው፣ ሌሎች ደግሞ በምንም ዐይነት አገር ቤት ውስጥ ገብተው በስራ ዓለም ላይ በመሰማራት ህዝብን እንዳያወናብድ መንገዱ ሁሉ መዘጋት አለበት። እነዚህ ሁሉ የዓለም አቀፍ ፋሺዝም መሰረቶችና ህዝብን የሚንቁ ስለሆነ በምንም ዐይነት ዕድል እንዳይኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል።
በአጭሩ የአራችን የኢኮኖሚ ችግር ሊፈታ የሚችለው መሰረታዊና ለሰፊው ህዝብ በሚጠቅሙ የምርት ክንዋኔዎች ላይ ስንሰማራና፣ ለሰፊው ህዝዝብ የሚጠቅሙ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል የማምረቻ መሳሪያዎች በማቅረብ ብቻ ነው። የተቀላጠፉ ሰፊው ህዝብ ካለምንም ጭንቀት ሊገለገልባቸው የሚችል የምርት ማምረቻ መሳሪያዎች ተመርተው ሲቀርቡ የአገራችንን የኢኮኖሚ ችግር መፍታት ይቻላል። ለዚህ የሚሆን ደግሞ የግዴታ በመንግስት የሚደገፍ ልዩ ዐይነት የክሬዲት ወይም የብድር ስርዓት መዋቀር አለበት። በሌላ አነጋግር፣ ዶላር የአንድ አገር የመገበያያ ገንዘብ ስለማይሆንና ለአንድ አገር ዕድገትም የማይጠቅም እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ዐይነቱ የተጨናገፈና አንድን አገርና ህዝብ ከሚያደኸይ፣ ከዚህም በላይ ጥገኛ ከሚያደርግ አስተሳሰብ የግዴታ መላቀቅ ያስፈልጋል።
በተለያዩ ምርቶችና በገንዘብ መሀከል የሚኖረው ግኑኝነት!
የአገራችን ኢኮኖሚ መሰረታዊ ችግር በተለያዩ የምርት መስኮች መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኘት አለመኖሩና፣ እነዚህ በገንዝብ አማካይነት አለመያያዘቸውና፣ በንግድ ውስጥ የሚሽከረከረው ገንዘብ ወደ ካፒታል ለመለወጥ አለመቻል ነው። እንደሚታወቀው አብዛኛው ህዝብ የሚተዳድረባቸውና ሰውነቱንም የሚጠግንባቸው የኢኮኖሚ መስኮች ከእጅ ወደ አፍ የሚታረስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና(Subsistence Farming) ኢንፎርማል መስክ(Informal Sector) የሚባለው ቁሳቁሶች የሚሸጥባቸው ናቸው። ከዚህም በላይ ሰፊው ህዝብ የሚዝናናባቸውና ዘመናዊ ከሚባለው መስክ ጋር ያልተሳሰሩ መዝናኛዎች አሉ። ዘመናዊ የሚባለው መስክ ደግሞ፣ ቀላል የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ እንደሱካር፣ የተለያየ ስም ያላቸው የቢራ ዐይነቶችን፣ የኮካኮላና የሚሪንዳ፣ የአልክሆል መጠጦች፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካና የጫማ ፋብሪካዎች ናቸው። የብስኩትና የስፓጌቲም ፋብርካዎች አሉ። አልፈው አልፈው መጠነኛ የሜታለርጂ ፋብሪካዎችም አሉ። ዘመናዊ ከሚባለው ውስጥ ደግሞ ተፈብርከው ወይም ተመርተው የሚሸጡትን ምርቶች ሰፊው ህዝብ እየገዛ የመጠቀም ኃይል የለውም። ይህም ማለት በዚህ ዐይነት የምርትክ ኢዱስትሪ የገበያ መስኩ የሚያድግና የሚስፋፋ አይደለም። ምናልባት ለብዙዎቻችን ግልጽ ያልሆነው ነገር እነዚህ ኢንዱስትሪዎች 1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በውጭ ኤክስፐርቶች አማካይነት የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ከአዲስ የፍጆታ አጠቃቀም ጋር ለማስተዋወቅ ሲባል የተቋቋሙ የምትክ ኢንዱስትሪዎች(Import Substitution Industrialization) በመባል የሚታወቁ ናቸው። እነዚህም ኢንዱስትሪዎች በተወሰነኑ ቦታዎች የተተከሉ ሲሆኑ የመባዛትና የማደግ ኃይል የሌላቸውና ለተሟላ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው። ከ1960ዎች አጋማሽ ጀምሮ ይታይ የነበረው የአገራችንም መሰረታዊ ችግር ከዚህ ዐይነቱ የተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ሞዴል ጋር የተያያዘ ነው። የካፒታሊስት አገሮችን የኢኮኖሚ ታሪክና የኢኮኖሚ ዕድገት በደንብ ያጠና ካለ ኢኮኖሚያቸውን በእንደዚህ ዐይነት መሰረቶች ላይ አልገነቡም። በጊዜውም አይታወቁም ነበር። የኢኮኖሚ ግንባታቸውን የጀመሩት ሌሎች ቅድመ-ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግና የማሽን ኢንዱስትሪ በማስፋፋትና ለጠቅላላው የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመቹ የቴክኒካልና የቴክኖሎጂ ኮሌጆችንና ልዩ ልዩ የማስልጠኛ ተቋማትን በመገንባትና በማቋቋም ነው። ዋናው ዓላማቸውም የተሟላና በማሽን ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ መከተል ሲሆን፣ ይህንን ለመደገፍ ደግሞ የራሳቸውን የባንኪንግ ስይስተም ወይም ስርዓት በመዘርጋትና የራሳቸውን ገንዘብ በማተም ብቻ ነው። እንግሊዝ በራሷ ገንዝብ ወይም ፓውንድ ነው የኢንስዱትሪ ፖለቲካ ማካሄድ የቻለችው። ፈረንሳይም ከእንግሊዝ በመማር ነው የራሷን ገንዘብ በማተም የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ማካሄድ የቻለችው። በኋላ ላይ የተነሳችው ጀርመንም የራሷን የባንክ ተቋም በመገንባትና ልዩ ዐይነት የክሬድት ስይስተም በመመስረት ነው ሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ አገር ለመሆን የበቃችው። መኪና በመጀመሪያ ጀርመን አገር የተፈጠረና የተስፋፋ ነው። ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስንና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችም ጀርመን አገር በመፈጠር ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ልዩ ልዩ አገሮች መስፋፋት የቻሉት። በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ 2/3ኛ የሚሆነው የኖቭል ዋጋ ተሸላሚ በ ያለው ጀርመን አገር ነው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ጠቅላላው የህብረተሰብ ግንባታ በሳይንሳዊ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታና በኋላ ላይ እያደገ የመጣው የህዝብ ፍላጎትና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እየገዙ መጠቀም ለገንዘብ በፍጥነት መሽከርከር መሰረት ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ ገንዘብ እንደገና ወደ ካፒታል በመለወጥ ወደ መዋዕለ-ነዋይ የመለውጥ ዕድል አገኘ። በሌላ አነጋገገ፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በገንዘበ አማካይነት የሚተሳስርና በገንዘብ የሚገለጽ በመሆኑ ገንዘብ ጥንካሬ ማግኘት ቻለ። በተለይም ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታና የቴክኖሎጂዎችም ማደግ አዳዲስ ምርቶችን፣ ለምሳሌው የልብስና የዕቃዎች ማጠቢያ፣ የቴሌቪዥን መስፋፋትና፣ ልዩ ልዩ የመኪና ሞዴሎች መመረታቸውና መሸጣቸው የካፒታሊዝምን ዕድገት ሲያፋጥን፣ በዚያው መጠንም የየአገሩ ገንዘብ ጥንካሬ ማግኘት ቻለ። ስለሆነም እንዚህ ዐይነት በሳይንስና በቴክኖሎጅ የሚገለጽ የኢኮኖሚ ስርዓት ያላቸው ገንዘባቸውን ከሌላው ጋር ሲወዳደር ዝቅ ማድረግ አያስፈልጋቸውም። ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚባሉትም በአገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ በመገንባት እንደዚህ አድርግ፣ ካላደረግህ ብድር አንሰጥህም እያሉ ተፅዕኖ የማድረግ መብትና ችሎታ የላቸውም።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ ይህ ዐይነቱ ሎጂካዊ ዕድገት ስለሌና ዝም ብሎ ብቻ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባል ነገር ስለሚታወቅ ጠቅላላውን ኢኮኖሚ በካፒታሊስታዊ ሎጂክ ላይ መመስረትና በቴክኖሎጂ ላይ እንዲመሰረት በማድረግ ልዩ ልዩ ምርቶችን ማምረት አልተቻለም። ስለሆነም እየመላለሱ አሁንም የምትክ ኢንዱስትሪ ተከላ በማድረግ ከ80% በላይ የሚሆነው ኢኮኖሚ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ እንዲመረት በማድረግ ተወስኖ እንዲቀር ተደረገ። በተለይም ከዛሬ ሰላሳ ሶስት ዓመት ጀምሮ የተያዘው ፈሊጥ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ አማካይነት የተቋም ማስተካከያ ፖሊሲ(Structural Adjustment Programs) የሚባለውን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ኢኮኖሚውን ማዘበራረቅ ነው። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ሳይንሳዊ ያልሆነና በታሪክ ውስጥ በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ አደጉ በሚባሉ አገሮች ውስጥና ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን እያመረቱ ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ ያልሆነ ነው። ራሱ የተቋም ማስተካከያ የሚባለውንም ስንምረመር በመሰረቱ የተቋም ማስተካከያ ሳይሆን ልዩ ችግሮችን የሚፈጥርና የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመክተት እዚያው በዚያው እንድንደፋደፍ የሚያደርገን ነው። በሌላ አነጋገር፣ የተቋም ማስተካከያ ፕሮግራም የሚባለው ነገር ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንድናመርት በፍጹም አላስቻለንም። የውስጥ ገበያ(Home Market) እንድናስፋፋ አላስቻለንም። የስራ መስክ ለሚፈልገው ሰፊ ህዝብ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል በፍጹም አልከፈተለትም። በተጨማሪም ፖሊሲው በተለያዩ መሰኮች መሀከል መተሳሰር እንዲኖርና፣ ገንዘብም በፍጥነት እንዲሽከረከር ሊያደርግ በፍጹም አላስቻለም። እንደሚታወቀው የአንድ አገር ኢኮኖሚ በምርት(Production)፣ በክፍፍል(Distribution) ወይም በደሞዝ ክፍያና በፍጆታ አጠቃቀም(Consumption) የሚገለጽ መሆን አለበት። ሰፊው ህዝብም በእየኢንዱስትሪዎችና በእርሻው መስክ ተመርተው ገበያ ላይ ወጥተው የሚሽጡትን ምርቶች ገዝቶ ለመጠቀም የሚችለው የመግዛት ኃይል(Buying Power) ሲኖረው ብቻ ነው። ይህ ከሆነ የገንዘብም በፍጥነት መሽከርከርና(Velocity of Money) ጥንካሬ ማግኘት ይችላል። በአጭሩ የአገራችን ዋናው የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ችግር የሚመነጨው ሎጂካዊ በሆነ መልክ ማሰብ ስለማንችልና በካፒታሊዝምና በተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚ ወይም የገበያ ኢኮኖሚ መሀከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ባለመቻላችን ነው። ስለሆነም የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የእነ ዓለም ባንክ መጫውቻ በመሆን ህዝባችንን ማደኽየትና አገራችንም ማፈራረስ ችለናል።
ከዚህ ዐይነቱ አጠር መጠን ብሎ ከተተነተነ ሁኔታ ስንነሳ የአገራችን የሞኔተሪ ችግር አንድን የኒዎ-ሊበራሊ ኢኮኖሚስት በሌላና የእነ ዓለም የገንዘብና የዓለም ባንክ ታዛዥ በሆነ ግለሰብ በመተካት ሊፈታ የሚችል አይደለም። ማሞ ምህረትን በኢዮብ ተካልኝ በመተካት የአገራችን የገንዝበ ችግር የሚፈታ አይደለም። ኢዮብ ተካልኝ የገንዘብ ሚንስተር ውስጥ በሚኒስተር ዲኤታ ተቀጥሮ ሲሰራ በ2020 ዓ. ም አገር ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ(Homegrwon Economy) የሚል ዕቅድ አውጥቶ ምንም ፋይዳ ያስገኘ አይደለም። በአገራችን ምድር የተስፋፋውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ ምንም ዐይነት የወሰደው እርምጃ የለም። ዝም ብሎ ብቻ አገር ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ ብሎ በማውራት ዕቅዱ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። ለማንኛውም ማሞ ምህረቱም ሆነ ኢዮብ ተካልኝ ባለፉት ሰላሳ ሶስት ዓመታት ብቻ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና በእነ ዓለም ባንክ ተረቆ የመጣውንና ተግባራዊ የሆነውን የተቋም ማስተካከያ ፕሮግራም በደንብ ያላጠኑና ችግሩም ከዚህ ዐይነቱ ፖሊሲና፣ ገንዘባችንን በተደጋጋሚ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ እንዲል በመደረጉና፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ የገንዝቡ የመግዛት ኃይል በአቅራቢና በጠያቂ መሀከል እንዲደነገግ በመደረጉ የተነሳ የተፈጠረና፣ በዚህም አማካይነት የውንብድና ስርዓት እንደተስፋፋ ሊረዱ የሚችሉ አይደሉም። ኢ-ሳይንሳዊና ታሪከ-አልባ በሆነ የኢኮኖሚ ትምህርት የሰለጠኑ በመሆናቸው ሰለካፒታሊዝም የውስጥ አሰራርና ሎጂክ የሚገባቸውም አይደሉም። ይሁንና እንደ አዋቂዎች በመምሰል የማያውቀውንና ስለህበረተሰብ አገነባብም ታሪክ ሊገባው የማይችለውን ሰፊውን ህዝብ የሚያሳስቱ ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን የነጭ ኦሊጋርኪው አሽከር በመሆን በህዝባችን ላይ የሚዘባነኑና የሚሳለቁም ናቸው። እንደነዚህ ዐይነቱ ዘመናዊ ፋሽሽቶች በእየአገሩ በመስፋፋት ነው ባህልንና ታሪክን የሚያወድሙት። አንድንም አገር የወንበዴዎችና የተለያየ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ በማድረግ ወጣቱ እንዲሳሳት የሚያደርጉ ናቸው። ይህ ዐይነቱን የብልግናና የውንብድና መስፋፋት የካፒታሊስት አገር መሪዎችና ጠቅላላው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚስት፣ የስለላና የሚሊተሪው ኤሊት የሚፈልገው ነው። እነዚህ ኤሊቶች፣ ባህል፣ ታሪክና ህብረተስብ ምን እንደሆኑ ስለማያውቁ ዓለምን ወደ አጠቃላይ ጦርነት በመለወጥ የበላይነታቸውን ይዘው ለመቆየት የሚፈልጉ ናቸው። ሃይማኖትን ከሃማኖት ጋር፣ አንዱን ጎሳ በሌላኛው በማስነሳት የበላይነታቸውን ይዘው ተዝናንተው ለመኖር የሚፈልጉ ናቸው። ሞራልና ስነምግባር የሌላቸውና በሌላው ደም ሀብት የሚያካብቱና አገር የሚያተረማምሱ ናቸው። በጥቂት ገንዘብ የማይጠግቡና በሙስና የተተበተቡም ናቸው። ስለሆነም የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ልንፈታ የምንችለው ጠለቅ ያለ ዕውቀትና የመንፈስ ጥንካሬ ሲኖረን ብቻ ነው። የአገራችን የኢኮኖሚ ችግር በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና ገንዘብን እየደጋገሙ ዝቅ በማድረግ የሚፈታ አይደለም። በተራ የሞኔተሪ ፖሊሲም የሚፈታ አይደለም። በተጨማሪም ዶላርን የመገበያያ ገንዘብ በማድረግም የሚፈታ አይደለም። እንደሚታወቀው ዶላር አሜሪካ ታትሞ ስለሚመጣ በክሬዲት በመዋዕለ ነዋይ ሊውል በፍጹም አይችልም። የወለዱ ሁኔታ(Interest Rate) በአሜሪካ የማዕከላዊ ባንክ የሚደነገግ ስለሆነ የኢትዮጵያ የማዕከላዊ ባንክ ምንም ዐይነት ተፅዕኖ አይኖረውም ማለት ነው። ዶላርን ዋናው የመገበያያ ገንዘብ ማድረግ ብሄራዊ ነፃነትን እንደመሸጥ ይቆጠራል። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የአንድን አገር ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው በራስ ገንዘብ ብቻ ነው። ህዝባችንን ተብተበውና የውጭ ኃይሎች ተገዢ በመሆን አገራችንን ወደ ጦር አውድማነት ከለወጡትና በጣም የቀጨጨ ጭንቅላት ካላቸው ሰዎች አገርችንና ህዝባችን መላቀቅ አለባቸው። እነዚህ ኃይሎች ከመብላትና ከመባለግ በስተቀር ምንም የሚያውቁት ነገር ስለሌለ ለአገር ግንባታ ሊያገለግል በፍጹም አይችሉም። መልካም ግንዛቤ!!
https://youtu.be/drv9Bcl1YQw?si=GyR-Vx2oDFp3HXR-
ማሳሰቢያ፣
የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በጥልቅና በተወሳሰበ ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። ፕሌቶ እንዳለው የሰው ልጅ ሁሉ ችግር የዕውቀትና በትክክል ያለማሰብ ችግር ስለሆነ የችግሮችም ምንጮች እነዚህ ናቸው። በአገራችንም ሆነ በተለያዩ አገሮች ያሉት ችግሮች አብዛኛውን ጊዜ ከፖለቲካ፣ ከሚሊተሪና ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ኤሊቶች የሚመነጩ ናቸው። ስለሆነም ለምንድነው ችግሮች በየጊዜው የሚከሰቱት እያሉ መጠየቅ ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ የአንድ አገር ችግር በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ የሚፈታ አይደለም። የፍልስፍና፣ የሶስዮሎጂና የህሊና ሳይንስና ሌሎችም ለጭንቅላት መዳበር አስፈላጊ የሆኑ ዕውቀቶች መስፋፋት አለባቸው። ቤተ-መጻህፍትም በየቦታው መዘርጋት አለባቸው። በአገራችንና በውጭው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ መጽሀፎችን የመግዛትና የማንበብ ልምድ የለውም። ሌላውና እስካሁን ግንዛቤ ያልተገባው ነገር ለአገርና ለህዝብ የሚደረግ ትግል ፕሮፌሽናሊትንና መተጋገዝን ይፈልጋል። በጥቂት ሰዎች አማካይነትና በትርፍ ሰዓት ብቻ እየጻፉ የአንድን አገር ችግር መረዳት በፍጹም አይቻልም። ሳይንሳዊና ዕውቀት አዘል፣ እንዲሁም ችግር ፈቺ ጽሁፎች በተከታታይ ሊወጡና ለንባብ ሊቀርቡ የሚችሉት ድጋፍ ሲኖር ብቻ ነው። አንድን ሳይንሳዊ ጽሁፍ ለማዘጋጀት የራስን ጊዜ መሰዋት ያስፈልጋል። ስለሆነም ድረ-ገጼን ለመጎብኘት ሞክሩ!!
መነበብ ያለባቸው መጽሀፎች፣
Arie Arnon; Money, Credit and the Economy: Monetary Theory and Policy From Hume
and Smith to Wicksell, New York, 2011
Augusto Graziani, The Theory of Monetary Circuit UK, 1989
Bernard Litear, Christian Arnspreger, Sally Goerner and Stefan Brunnhuber;
Money and Sustainability, Berlin, 2011
Frederick G , Lawrence, Patrick H. Byrne, and Charles C. Hefling, Jr;(eds.) Macreonomic
Dynamics : Essays in Circulation Analysis: Collected Works of Bernard
Lonegan, Canada, 1999
Jacob Soll; Free Market: The History of An Idea, New York, 2022
Karl Marx; Capital: A Critical Analysis of Capitalist Production, Vol. 1, 2 &3, USA, 1975
Nassim Nicholas Taleb; The Black Swan: The Impact of the Highly Improbable, On
Robustness and Fragility New York, 2007
Paul Mattick; Marx and Keynes, Frankfurt am Main, 1971
Richard Arena & Neri Salvadori(eds.) Money, Credit and the Role of the State, Great
Britain, 2004
Thomas Piketty; Capital in the Twenty-First C
