[gtranslate]

የዶ/ር አቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ- ለስር-ነቀል የሚያመች ሁኔታ

ወይስ ትግሉን የሚያደናቅፍ  ?

                                                                                     ፈቃዱ በቀለ  (/)

                                                                                     ሚያዚያ 23 2018

 

መግቢያ

ሰሞኑን የዶ/ር አቢይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒሰተር ሆኖ መመረጥ በተለይም ውጭ አገር ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። አንዳንዶቹ እንደዚህ ዐይነቱ ብሩህ ሰውና በግልጽ የሚናገር ኢትዮጵያዊ ምሁር ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጡ እግዚአብሄር ከሰማይ እንደላከው መታየት ያለበትና፣ አገራችንና ህዝባችን ለገጠማቸው የተወሳሰቡ ችግሮች መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ነው ብለው ይደመድማሉ። በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ደግሞ ምንም ምክንያት ሳያቀርቡ፣ እንደዚህ ዐይነቱ የተለሳለሰ ሰው ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጡ ትግሉን ያዳፍነዋል ይላሉ። ይሁንና ግን ትግል ሲሉና የትግል ዓላማውስ የመጨረሻ መጨረሻ በምን መልክ መታየትና መመንዘር እንዳለበት አይነግሩንም። በሶስተኛ ደረጃ የሚቀርበው አስተያየት ደግሞ፣ የዶ/ር አቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ ሆን ተብሎ የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም የተደረገ ሴራ(Conspiracy) ነው ብለው የራሳቸውን ድምዳሜ ይሰጣሉ። በአራተኛ ደረጃ የሚቀመጠው አስተያየት፣ እንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጡ ጥሩ ነው።  አገራችንም የሚያስፈልጋት እንደዚህ ዐይነቱ ውስጠ-ኃይል ያለው መሪ ነው ብለው ሲናገሩ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ሰው ያሰበውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ የግዴታ ድጋፍ ያስፈልገዋል፤ ሰውየውን የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም እንደተደረገ ሴራ አድርጎ ማየቱ ችግሩን ውስብስብ ከማድረጉ በስተቀር ሌላ የሚያመጣው መፍትሄ የለም። ስለሆነም ይላሉ እነዚህ ዐይነቱ ግለሰቦች፣ የዶ/ር አቢይ አህመድን መመረጥ እንደጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ የራስን አስተያየት በማከል ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና እኩልነት እንዲሁም ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊሰፍንበትና ሊዳብርበት የሚችል ስርዓተ-ማህበር  እንዲፈጠር የራስን አስተዋፅዖ ማበርከት ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ነው ብለው ይናገራሉ።

ወደ አገር ቤት ስንመጣ ህዝባችን በዶ/ር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ የመንፈስ ደስታ እንደተሰማውና መተንፈስም እንደጀመረ እንመለከታለን። ለአርባ ዐመት ያህል ብጥብጥና ግድያን እንዲሁም የጥይት ጩኸትን፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት 27 ዐመታት ከፍተኛ ሰቆቃ የደረሰበትና መግቢያና መውጫ እንዲያጣ የተደረገ ህዝብ እንደዚህ ዐይነቱ ብሩህ የሆነ ኢትዮጵያዊ ምሁር ሲመረጥ እንደ እግዚአብሄር ፀጋ አድርጎ ማየቱ የሚያስገርም ነገር አይደለም። ይህም ማለት እኛ ውጭ አገር በደንብ በተዘጋጀና ሰላም በሰፈነበት ዓለም የምንኖርና፣ ስንትና ስንት ስቃይ እያየ አገር ውስጥ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ መሀከል ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት መከሰቱ የሚገርም አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ በደንብ እንደተገነዘበው የዶ/ር አቢይ መመረጥ ጥሩ የሆነውን ያህል ከፍተኛ ድጋፍ ካልተሰጠው በስተቀር  ብቻውን  ወደፊት እንደማይገፋ በግልጽ ይናገራል። ስለዚህ ትግሉ እሱ በመመረጡ የሚቆም ሳይሆን መቀጠል እንዳለበት ለህዝባችን ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። ከዚህ ስንነሳ እንደሚጠበቀውና እንደሚገመተው ዶ/ር አቢይ በጥቂት ቀናት ተዓምር ሊፈጥር አይችልም። ወያኔም የሚያደርገውን ጭፍጨፋና አፈና በአንድ ጊዜ ለማስቆም እንደማይችል ሰሞኑን የምንሰማውና የምንከታተለው ነው። ስለሆነም የእኛ ሚና ምን መሆን አለበት ? በሚለው ላይ የራሴን አስተያየት ከመስጠቴ በፊት ከታሪክ ማህደር አንዳንድ ነገሮችን ማንሳት እፈልጋለሁ።

 

አንዳንድ የታሪክ ትዝታዎች !

የየካቲቱ አብዮት በ1966 ዓ.ም ሲፈነዳ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የደገፈውና ለለውጥም የተዘጋጀ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ የተወሰዱትን እንደመሬት ላራሹና የማሰተማር ዘመቻውን ህዝቡ ሆ ብሎ ነው የተቀበለውና የደገፈው። ይሁንና ግን  በጊዜው የመሬት ላራሹም ሆነ የከተማ ቤቶች ካለምንም ካሳና መደገፊያ ሲወረሱ ስህተት አልተሰራም ማለት አይደለም። የገጠር መሬትም ሆነ የከተማ ቤቶች ሲወረሱና መፈክርም ሲንጋጋ በተለይም የመሬት ባላባቱንና፣ በአጠቃላይ አነጋገር ንዑስ ከበርቴ የሚባለውን መደብ እንዳስደነገጠውና ወደ ማይሆን ግብግብ ውስጥም እንደከተተው የማይካድ ሀቅ ነው። በወቅቱ ሰፋ ያለ የፖለቲካና የሶስይሎጂ ትንተና በመስጠት ችግሩን በሌላ መልክ ለመፍታት ከመቃጣት ይልቅ የተያዘው ፈሊጥ በስድብና በዛቻ፣ እንዲሁም በጥይት ለመፍታት ነው የተሞከረው። አብዮቱን ያልደገፈ ወይም በጥርጣሬ የተመለከተ ሁሉ እንደ አድሃሪ በመታየቱ ህዝባዊ ቅራኔ እየሰፋ መጣ። ከዚህም ባሻገር ምንም ዐይነት የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና የሌላቸውና ያልበሰሉ ኃሎች እዚህና እዚያ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ወስጥ  እየተመለመሉ በመግባታቸው  ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እንዲፋፋም አደረጉ። ብዙ የዋህ ህዝብና ወጣት ትውልድ ህይወቱን እንዲያጣ አደረጉ። በተለይም ደግሞ  „የእኔን አዋጅ ቀሙብኝ“  በማለት የተበሳጨው ራሱን ተራማጅ ነኝ ብሎ የሚጠራው ኃይል በጊዜው የተፈጥረውን አዲስ የፖለቲካ ሁኔታ ከሳይንስ አንፃር ከመገምገምና ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩ የባሰውን ውስብስብ እንዲሆን ጥይት መተኮስና ማተረማመስ ጀመረ። ይህ ዐይነቱ ነገሮችን ረጋ ባለ መልክ ለማየት አለመቻልና ሰፋ ያለ በሳይንስ ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካዊ ትንተና መስጠት ባልተለመደበት አገር መፍትሄው ጦርነት ብቻ ነው ብሎ የተነሳው አንድ ኃይልና ከዚያ በኋላ እንደ አሽን የፈለቁ የነፃ አውጭ ድርጅቶች ነን ባዮችና፣ የውስጥ ለውስጥ አሻጥር ሰሪዎች በህዝባችንና በታሪካችን ላይ ሁለንታዊ ጦርነት በማወጅ በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት የተወሳሰበ ሁኔታ ፈጥረው ለመሄድ ቻሉ። ይሁንና ግን እነዚህ ኃይሎች ከስህተታቸው አንድም ትምህርት ሳይቀስሙ የሰራነው ሁሉ ትክክል ነው፤ ካለኛ በስተቀር ለአብዮቱ ደሙን ያፈሰሰ የለም በማለት እስከዛሬ ድረስ በቂም በቀልና በጥላቻ በመታወር አሁንም እየታገልን ነው ይሉናል። ለምድን ነው የምትታገሉት ስንላቸው ? ለመሰረታዊ ለውጥ ነው ይሉናል። መሰረታዊ ለውጥስ እንዴትስ ነው ሊመጣ የሚችለው ? ሲሏቸው ወያኔ ሲወድም ነው ይሉናል። በዚህ ላይ ብንስማማም፣  በምን ስትራቴጂና የፖለቲካ ፍልስፍና በመመርኮዝ ነው ወያኔን ከስልጣን በማስወገድና የገነባውን ጨቋኝ ስርዓት በማንኮታኮት ዲሞክራሲያዊና ለህዝብ ተጠያቂ የሚሆን መንግስት መገንባት የሚቻለው ? ብለን ጥያቄ ስናቀርብ ስልጣን ስንይዝ እናሳይሃለን በማለት ነገሩን አድብሰብሰው ያልፋሉ። ይሁንና ግን የሚዘነጉት ነገር ከ40 ዐመት በኋላ አዲስ ትውልድ እንደተፈጠረና የዓለምም ሁኔታ እንደቀድሞው ሳይሆን በብዙ አኳያ እንደተለወጠና አንድን አገር ለመገንባትና የሰፊውን ህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ የግዴታ በፍልስፍና፣ በቲዎሪና በሳይንስ የመታጠቅን አስፈላጊነት የተረዱ አይመስለኝም። በተጨማሪም በአንድ አገር ግንባታ ውስጥ ብሩህና ግልጽ አስተሳሰብ ያላቸው ምሁራን በሙሉ መሳተፍ እንዳለባቸው የተገነዘቡ አይደሉም።

ሁለተኛው  የታሪክ ስህተት ወያኔ ስልጣን ላይ ሲወጣ የተሰራው ስህተት ነው። በመጀመሪያ ወያኔ በራሱ ኃይል ስልጣን ላይ የወጣ ሳይሆን በጊዜው የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀምና ሲአይዔ(C.I.A) ስላገዘው ብቻ ነው። ለወያኔ ስልጣን ላይ መውጣት ከሲአይዔ ጋር ይሰሩ የነበሩና፣ አብዮቱ እንደፈነዳ እየተመለመሉ ወደ አገር ቤት የገቡ የወታደሩ አባሎች ወይም መኮንኖችም ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ የሚታወቅ ነገር ነው። የወያኔ የሜዳ ወታደር ነው ያንን ያህል ግዙፍና በመቶ ሺሆች የሚቆጠረውን የደርግ ሰራዊት አንኮታክቶ የጣለው ብሎ ማናፈስ ተረት ነው። ታሪካዊና ሳይንሳዊ ማስረጃ የሌለው አነጋገር ነው። ስለሆነም ወያኔ በምንም ተዓምር ጭንቅላቱን በማነፅና በከፍተኛ ዕውቀት በመታገዝና በመኮትኮት ከሌላው ጋር በመተባበር ለአጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ለውጥ የታገለ ሳይሆን የራሱን አጀንዳ ይዞ በመነሳትና የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን በመከተል አገራችንን በሁሉም አቅጣጫ ለመሽንሽንና ለማዳከም ቆርጦ የተነሳ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ኃይል ለመሆኑ ባለፉት 27 ዓመታት ብቻ ካካሄደው የትርምስ ፖለቲካ መረዳት ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ ወደተሰራው ስህተት ስንመጣ፣ በጊዜው ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ከጥቂት ወራት በኋላ የወያኔን ስልጣን መውጣት አስመልክቶ በተለይም እዚህ ውጭ አገር ከፍተኛ እንቅስቃሴና ተቃውሞ የሚታይበት ወቅት ነበር። በተለይም የትግሉ መሪዎች ነን የሚሉ በአብዮቱ ወቅት የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት ከመቅጽበት በመርሳት የጨለማ ጊዜ እንደመጣ አድርገው ነበር የተመለከቱት። ይህንን አስመልክቶ እዚህ ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ውስጥ በፈረንጆች አቆጣጠር በበጋው ወራት በ1991 ዓ.ም ትልቅ ሰላማዊ ስልፍ ይደረጋል። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ አገሮች በመምጣት ለሰላማዊ ሰልፉ ድምቀት ሰጥተውት ነበር። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የመኢሶንና የኢህአፓ  መሪዎችም ተገኝተው ነበር። አንዳንዶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በዐይኔ ለማየት የበቃሁትና የኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ትንተናን ለማዳመጥ የቻልኩት። ለማንኛውም የአብዛኛዎቹ ሀተታና ድምደማ ወያኔን ማውገዝ ነበር። ይህ ዐይነቱ ሀተታ ደስ ስላላለኝና ዝም ብሎ ወደ አጠቃላይ ተቃውሞ ከመምጣት በሚል የራሴን አስተያየት ለመስጠት ሞከርኩ። የእኔ አቀራረብ ዝም ብሎ በጭፍን በጥላቻ ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ከማካሄድ ይልቅ በመጀመሪያ ደረጃ ሁላችንም አገራችን ለገባችብት የተወሳሰበ ችግር ተጠያቄዎች እንደመሆናችን መጠን የግዴታ ሁኔታውን በጥሞና መመልከት ያስፈልጋል የሚል ነበር። ይህንን አስተያየት ከሰጠሁ በኋላ እንደ ትልቅ ጠላት በመታየት አንዳንዶች ውርጅብኝ አወረዱብኝ። በዕውነት በጣም ተደናገጥኩኝ። የኋላ ኋላ ሌላውን አክራሪ ነው እያሉ የሚሳደቡ በጊዜው ይሰነዝሩ የነበረው አስተያየት ከአክራሪም በላይ የሆነ አነጋገር ነበር። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ወደ ምሽት ገደማ ብዙዎች አንድ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ይሄዳሉ። እኔም እስቲ ልውጣ በማለት ከባለቤቴ ጋር እንሄዳለን። ምድረ ኢትዮጵያዊ ሬስቶራንቱን ሞልቶት ነበር። ምግብ አዘን በልተን ከጨረስን በኋላ አንዱ መቀመጫችን ጋ በመምጣት አንተ ፀረ-ኦሮሞ መሆንህን ቀድሞም ሰምቻለሁ ብሎ ያልሆንኩትንና አስቤም የማላውቀውን ነገር ይነግረኛል። ትዝ እስከሚለኝ ድረስ ሰውየው ስዊድን አገር የሚኖር ነበር። እኔም በነገሩ በመገረም ምንም ሳልናገር ነገሩን ለማደባበስ ሞከርኩኝ። በነገራችን ላይ ሰላማዊ ሰልፉና ውይይቱ ፀረ-ወያኔ ነበር እንጂ ፀረ-ኦሮሞ አልነበረም። በጊዜውም የኦኤል ኤፍ (OLF) መሪዎች ከወያኔ ጋር በመሆን ስልጣን የጨበጡበት ጊዜና የኦሮሞን ብሄረ-ሰብ መብት እናስከብራለን ብለው ደፋ ቀና የሚሉበት ወቅት ነበር። ያም ሆነ ይህ የሰውየውን አባባልና እኔን „የኦርሞን ብሄረሰብ ይጠላል“ ብለው የነገሩትን ሰዎች ሎጂክ እስከዛሬ ድረስ በፍጹም ሊገባኝ አልቻለም።

ለማንኛውም በጊዜው የተከሰተውን ሁኔታ በሰፊው በመገምገምና በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍና በመታጠቅና በመደራጀት አማራጭ መፍትሄ ከማቅረብ ይልቅ ወያኔን ኮርነር ውስጥ ለማስገባት የተደረገው ስትራቴጂ በፍጹም አልሰራም። የኋላ ኋላ እነዚህ እኔን በንቀት የተመለከቱኝና ያኮረፉኝ ኃይሎች ከወያኔ ጋር እንደራደር በማለት ግብግብ ነው የተያያዙት። እስከ አዲስ አበባ ድረስ በመዝለቅ ለመደራደር ሞክረው ነበር። ይሁንና ግን ወያኔ የልብ ልብ እየተሰማው የመጣበት ጊዜ ስለነበር ለመደራደር ዝግጁ አልነበረም። ያም ሆነ ይህ ከነዚህም ሆነ ከሌሎች ኃይሎች የተከፈተው ወያኔን የመጣል ዘመቻ ቀስ በቀስ ወያኔን በማጠንከር በዚያው መጠንም የጥፋት ኃይሉን እንዲሰነዝር ነው የረዳው። እኔም ራሴ በጊዜው ከትንሽ አርቆ አስተዋይነት በስተቀር እንደዛሬው በፖለቲካም ሆነ በቲዎሪ ብዙም የገፋሁ ስላልነበርኩ ለጊዜው ረጋ ባለ መልክ ጥናት ማካሄድ ላይ ነበር እንዳተኩር የተገደድኩት።

ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በተለይም በኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ በማትኮር በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ አማካይነት ተጠናቅሮ የመጣውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠጋ ብዬ በመመርመር ይህ ፖሊሲ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥር እንደማይችልና እንዳልቻለ፣ በአንድ በኩል ጥቂቱን በማደለብ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፊውን ህዝባችንን ወደ ድህነት እንደሚገፈትረውና እንደገፈተረው ለማመልከት ሞክሬአለሁ። በተጨማሪም ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የሚመጣ ሳይሆን፣ አንድ አገር ልትብለጽግና የህዝቡም ኑሮ ሊሻሻል የሚችለው ሁለንታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማካሄድ ብቻ ነው በሚል ትክክል ነው ብዬ የማምንበትንና ሳይንሳዊ መሰረት ያለውን አስተያየቴን ለመሰንዘር ሞክሬያለሁ። ስለሆነም ሰፋ ላለ የኢኮኖሚ ዕድገት የግዴታ ለፈጠራ የሚያመች የማኑፋክቱር አብዮት ማካሄድ እንደሚያስፈልግና፣ ይህና የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መተሳሰር እንዳለባቸውና፣ በዚህም መሰረት ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት(National Wealth) እንደሚፈጠር ለማመልከት ሞክሬያለሁ። ለማረጋገጥ እንደሞከርኩትም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ተጠናቅሮ ወያኔ ተግባራዊ እንዲያደርግ የተሰጠው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሰፋ ያለ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባት አላስቻለም። አገሪቱን ከድህነት አለማላቀቁ ብቻ ሳይሆን በዕዳ እንድትተበተብና የውጭው የንግድ ሚዛንም በከፍተኛ ደረጃ እንዲዛባ ለማድረግ የበቃ አደገኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። በመሰረቱ ኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን አገር አፍራሽና ህዝብን የሚያደኸይ ነው።  የአንድን ህዝብ ነፃነት የሚገፍና ብሄራዊ ሀብት የሚያወድም ነው። ለመንግስትም አስተማማኝ የሆነ ሰፋ ያለ የቀረጥ መሰረት(Tax Base) ሊፈጥር አይችልም። በዚህም ምክንያት ይህንን ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርግ መንግስት በበቂ ባጀት ችግር የተነሳ  የግዴታ በውጭ ዕርዳታ እንዲተማመን ይደረጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን  ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት የሌለው አገርና የመንግስቱም ገቢ አስተማማኝ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ የግዴታ የማህበራዊና ሌሎች መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች ሊመለሱ ወይም ሊፈቱ አይችሉም። አንድ መንግስት ብቃትነት ባለው ሁኔታ ማንኛውንም ማህበራዊ ችግሮች ሊፈታ የሚችለው አንድ አገር በስነ-ስርዓት የተደራጀ የውስጥ ገበያ(Home Market) ሲኖረውና፣ የሰፊው ህዝብም የመግዛት ኃይል(Buying Power) እያደገ የመጣ እንደሆነ ብቻ ነው። ስለሆነም የሰፊው ህዝብ ገቢ ሲያድግ መንግስትም ከቀረጥ የሚያገኘው ገቢ ስለሚጨምር ለማህበራዊ መስክ የሚመድበው ድጎማና ለምርምርና ለሌሎች ፕሮጀክቶች የሚያወጣው ወጪ አስተማማኝ ይሆናል ማለት ነው። የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግን የተቃራኒውን የሚያደርግ ነው።

የወያኔን የኢኮኖሚና የሶሻል ፖሊሲ በሚመለከት የዚያን ጊዜ በንቀት ከተመለከቱኝና ካንቋሸሹኝ ታጋዮች አንዳችም ክሪቲካል ጥናት አልቀረበም። አንዳንዶቹ ወደ ስድብ ሲያመሩ፣ ሌሎች ደግሞ ገለጻ ከመሰጠት በስተቀር በፍልስፍና፣ በቲዎሪና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ፍቱን ሀተታና መፍትሄ ሲሰጡ አላየሁም። በምን ተዓምርም ለመሰረታዊ ለውጥ እንደሚታገሉ ግራ አጋብተውኛል። ያም ተባለ ይህ በአንድ አገር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የግዴታ በቲዎሪ፣ በሳይንስና በፍልስፍና መታጠቅን የሚጠይቅ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም መሰረታዊ ለውጥ በክንውን ወይም ኢቮሉሺነሪ በሆነ መንገድ የሚመጣ እንጂ አንድ ቦታ ላይ በመጫን ወይም ህዝብን ለመሰረታዊ ለውጥ ተነሳ በማለትና በመቀስቀስ የሚመጣ አይደለም። ከአገራችን የአብዮት ታሪክና ከሌሎች አገሮች ልምድም የምንማረው ተፈጥሮ መዝለልን እንደማታውቅ ሁሉ(Friedrich Schiller)፣ አንድ ህብረተሰብም ከአንድ ስርዓት ወደ ሌላ የተሻለ ስርዓት ከመቅጽበት በፍጹም ሊሸጋገር አይችልም። በተለይም ደግሞ ለብዙ መቶ ዐመታት ስር የሰደደ ፊዩዳላዊ ባህል የሰውን ጭንቅላት ቆልፎ በያዘበት አገር ውስጥ የሚደረገው ትግል ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። አብዮትን በሚፈልገውና ለውጥን በሚጠላው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል ግብግብ ስለሚፈጠር የታሰበው ዓላማ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። በሌላ ወገን ደግሞ ራሳቸው አብዮትን አመጣለሁ ብለው የሚታገሉ ኃይሎች የጭንቅላት ተሃድሶን ስለማያደርጉና ዕውነተኛ ነፃነትም በምን መሰረተ-ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ እንደሆን ስለማይገነዘቡ ክፖለቲካ ውይይትና ክርክር ይልቅ ወደ አመጽ ያመራሉ።  በዚህም ምክንያት የተነሳ ጥራት ካለውና ወደ መፍትሄ ከሚያመራ የሰከነ ትግል ይልቅ ሁኔታው ውስብስብ በመሆን መሰረታዊ የህብረተሰብ ጥያቄዎች ሊፈቱ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስልጣኔ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደብዛቸው እንዲጠፋ በማድረግ አንድ ህዝብ በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖር ይገደዳል። በአብዮትም ወቅትና በኋላም የተፈጠረው ይህ ሁኔታ ነው።

በሶስተኛ ደረጃ በሌላ መልክ ወደ ተሰራዉ ስህተት ስመጣ አሁንም የምገነዘበው ሀቅ ጥቂት ትዕቢተኞችና ሌላውን እንዳላዋቂ የሚቆጥሩና፣ ከአገራቸው ምሁራን ይልቅ ነጭን የሚያመልኩ በሚሰሩት የታሪክ ወንጀል የአንድ ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን የተከታታዩም ትውልድ ዕድል እንዴት እንደሚበላሽ ነው። እነዚህ ጊዜው  የኛ ነው ብለው እዚህና እዚያ የሚሯሯጡ ኃይሎች ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ጥናትን መሰረት አድርገው ከመታገል ይልቅ በራሳቸው የጥቅም ፍላጎት በመመራት ከአንድ የፖለቲካ ስህተት ወደ ሌላ በመሸጋገር የህዝብን ኃይል ይበታትናሉ፤  የስልጣኔንም ትርጉም እንዳይረዳ ያደርጋሉ። ስለሆነም ትግል የሚባለው መፈክር አንድ ቦታ ላይ መቋጠሪያ የሌለው ዘለዓለማዊ ትርምስን የሚፈጥር በመሆን አንድ ህዝብ ግራ ተጋብቶና ጨልሞበት እንዲኖር ያደርጋሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ በግንቦቱ 1997 ዓ.ም ምርጫ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ የወጣበትና በአገዛዙ ላይ ያለውን ጥላቻ በማረጋገጥና በማሳየት ቅንጅትንና ህብረትን የመረጠበት ታሪካዊ ወቅት ነበር። በጊዜው ይህ ዐይነቱ ታሪካዊ የህዝብ ድል የውሃ ሽታ ሊሆን የበቃው አንዳንዶች እንደሚሉት በወያኔ አሻጥር መስራት ሳይሆን፣ በተለይም በአንዳንድ የቅንጅት መሪዎች ስልጣን ስግብግብነት የተነሳና፣ አሜሪካንና የተቀረውን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን በማመንና  በእነሱ አማካሪነት ስልጣን ላይ እንወጣለን ብሎ በመቋመጥ ነው። እዚህ መጥተው ያሰተናገድናቸው የቅንጅት መሪዎችና እስከውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ድረስ በመውሰድ እንደ አስተርጓሚ በመሆን የረዳናቸው የኋላ ኋላ እኛ የነገርናቸውን ሳይሆን እነ ቲም ክላርክ የመከሯቸውን ምክር በመከተል ነው ህዝባችንን የባሰ ችግር ውስጥ የከተቱት። ከዚያ በኋላ የወያኔ አገዛዝ ፋሺስታዊ በሆነ መንገድ በስናይፐር እያነጣጠረ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያንን ከገደለ በኋላ አገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንጥራ አንጥራ በሚለው ላይ ቲአትር ሲሰራ ነበር። በህዝቡ ዘንድ ከፈተኛ የሆነ የቆራጥነት ስሜት ቢኖርምና ወያኔም በከፍተኛ መርበትበት ላይ ቢገኝም፣ የቅንጅትና የህብረት መሪዎች የህዝቡን ፍላጎት በመናቅ የቤት ውስጥ አድማ እናድርግ በማለት የሰፊውን ህዝብ ሃሞት ወደማፍሰስ አመሩ። የህዝቡን ቆራጥነት የተገነዘበውና የቅንጅትና የህብረት አመራሮችን ልብ ያነበበው መለሰ ዜናዊና የውጭ ኃይሎች ካለምንም ቅድመ-ሁኔታ መነጋገር እንችላለን በማለት ለውይይት ዝግጁ እንደሆነ በእነቲም ክላርክ አማካይነት ለቅንጅት መሪዎች መልዕከት ላከ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሶስት ቀን ያህል የቤት ውስጥ አድማ ይደረጋል የተባለው እንዲታጠፍ ተደረገ። ይህንንም ለሰፊው ህዝብ ያስታወቀው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ነበር። እንደተባለው ከመለስ ዜናዊ ጋር ለመወያየትና አንድ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተመርጠው የገቡት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ነበሩ። በውይይቱ ላይ መለሰ ዜናዊ ገንቢ የሆነ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ በማስፈራራትና በመስደብ ነው ስብሰባውን ጥለው እንዲወጡ ያደረጋቸው። ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ነገሩ አስቸጋሪና እንደማይቻል በወቅቱ ለጋዜጠኞችም ሆነ በዚያ ለተሰበሰበው ህዝብ ለማስረዳት ችሏል። ይሁንና ይህን ሁኔታ በመገንዘብና የአገዛዙንም መፍረክረክ ቁጥር ውስጥ በማስገባት አገዛዙን ለማስወገድ ስትራቴጂ ከማውጣትና በጋራ ለመታገል በቆራጥነት ከመነሳት ይልቅ የስልጣን ሽኩቻ በማድረግ የኋላ ኋላ ወያኔ ሊረጋጋና ስልጣኑን ሊያጠንክር የሚችልበትን አመቺ ሁኔታ ፈጠሩለት። ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ ? የቅንጅት መሪዎች እንዳሉ ታፍሰው ወደ እስር ቤት ተወረወሩ። በዚያው መጠንም ወያኔ የባሰውን ኃይሉን በማጠንከርና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጉያ ስር ጠቅልሎ በመግባት በህዝባችን ላይ አጠቃላይ ጦርነት አወጀ። በዚያው መጠንም በኒዎ-ሊበራሊዝም ፖሊሲ አማካይነት የተቀዳጀውን የኢኮኖሚ የበላይነት በማጠንክር ህዝቡን መላወሻ በማሳጣት የራሱን ኢምፓየር ገነባ። ይህ እየጣመው ሲሄድና፣ ኃይሉንና ሀብቱን ላለማስነካት በማለት የባሰ ዘረፋ ውስጥ በመግባት የህዝባችንን ሰቆቃና የወጣቱን ከአገር ውስጥ መሰደድ በማባባስ አገራችንና ህዝባችንን የባሳ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ከተታቸው። ከዛሬ ሶስት ዓመታት ጀምሮ በኦሮሞና በአማራው ክልል፣ በተለይም በጎንደር የሚካሄደው ትግልና ወያኔ የሚያካሄደው ፋሺሽታዊ  ግድያዎች የእነዚህ ድምር  የፖለቲካ ስህተቶች ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። የቲዎሪ፣ የፍልስፍናና የሳይንስ ጥራት በሌለበት አገርና በአወቅሁኝ ባይነት የሚካሄድ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ የአንድን ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን የሶስትና የአራት ትውልድን ዕድል እንደሚያበላሽ መገንዘብ እንችላለን። በተለይም ትዕቢትና መናናቅ በበዛበትና፣ የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ሁኔታ በደንብ ሳያጠኑ የሚካሄድ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ መቀመቅ ውስጥ ነው የሚከተን። የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ለመረዳት የማይችል፣ እንዲሁም ደግሞ ሳይንስን፣ ፍልስፍናንና ቲዎሪን መሰረት ያላደረገ ትግል የሚሉት ፈሊጥ ነገር የባሰ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከተን ከአገራችን የአርባ ዓመት የትግል ታሪክ ብቻ ሳይሆን ከብዙ አገሮችም ታሪክ የምንረዳው ጉዳይ ነው። በአንድ አገር ውስጥም ሰላምና መረጋጋት ሊመጣ የሚችለው በትንሽ ዕውቀት ወይም በክስተት ላይ በተመሰረተ ዕውቀት በመመካትና በመናናቅ ሳይሆን በመደማመጥ ብቻ ነው። ከታላላቅ ፈላስፋዎች፣ የቲዎሎጂና የሶስዮሎጂ ተመራማሪዎችና የተፈጥሮ ሳይንስ አዋቂዎች የምንማረው ነገር ክስተታዊ ዕውቀት ወደ ጨለማና ወደ ዘለዓለማዊ ጦርነት እንደሚያመራን ነው። ይህንን በሚመለከት ፕላቶንም ሆነ ላይብኒዝ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመት በፊትና በ17ኛው ክፍለ-ዘመንም አስጠንቅቀዋል።  ስለሆነም የሌላ ሰውን ሃሳብ የማይሰሙ ታጋይ ነን ባዮች የአንድን አገር ታሪክ ያበላሻሉ። የሚጎዳው ግን፣ „መቼ ነው ከጨለማው ዓለም መውጣት የምችለው“ ብሎ የሚጸልየው ሰፊው ህዝብ እንጂ በዚህም በዚያም ብሎ አምልጦ ከወጣ በኋላ ታጋይ ነኝ በማለት ሜዳውን የሚሞላው አይደለም። ክዚህ ድምር ስህተት ስነነሳ የዶ/ር አቢይን ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ እንዴት ነው የምገነዘብው ? ከሱስ የምንጠብቀው ነገር ምንድነው ? ይህንን ከመቃኘቴና የራሴን የመጨረሻ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት አንዳንድ ነገሮችን ላንሳ።

 

ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጠሩ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሁኔታዎች !

ትልቁ የፖለቲካ ጥበብ በየኢፖኩ የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎችን በመገምገም የሰከነ ፖለቲካ ማካሄድ ነው። እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ አንድ ዐይነት አመለካከትና ጥቅም ሊኖረው በፍጹም አይችልም። አንድንም ህዝብ አንድ ዐይነት አመለካከት መያዝ አለብህ ብሎ ማስገደድ የፈጠራን ስራ ማስተጓጎልና ግለሰብአዊ ነፃነትን እንደማፈን ይቆጠራል። ስለሆነም ወደድንም ጠላንም ህብረተሰብአዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች(Social Realities) የሚባሉ ነገሮች አሉ። እነዚህም የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግኑኝነቶች፣ ለምሳሌ የሀብትና የይዞታ ጉዳይ፣ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ የፍጆታ አጠቃቀም ጉዳዮችና በዕውቀት ማነስ የተነሳ የሚፈጠሩ ህብረተሰብአዊ የእሴት እጦቶችና በተለያየ መልክ የሚገለጹ አደገኛ ባህርዮች ናቸው። በተለይም ሰፋ ያለ  በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ክንዋኔና፣ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ባልዳበረበት አገር ውስጥ፣ እንዲህም በተለይም ከላይኛው የህብረተሰብ ክፍል ህብረተሰብአዊ እሴቶች ሲጣሱ ይህንን በሳይንስና በፍልስፋና፣ እንዲሁም በውይይት ለመግታትና ለመፍታት ልምድ በሌለብት አገር ውስጥ አንዳንዶች የኦሊጋርኪ ባህርይ በማዳበር አንድ ህብረተሰብ እንዲናጋ ያደርጋሉ። በደሃና በሀብታም መሀክል ያለው የሀብትም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት ስለማይጣጣሙ ይህ ሁኔታ በተለያየ መልክ ለሚገለጽ የሰላም እጦትና እርገጠኛ ሆኖ በመንገድ አለመንቀሳቀስ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ  በተለያየ የታሪክ ወቅት ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ለህዝባችን አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሰረት ሊጥሉ አልቻሉም። የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተላቸው ሰፋ ያለ ለፈጠራ የሚያመች የስራ-ክፍፍል እንዲዳበር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር አልቻሉም። ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መሰረት የሚሆኑ የመዋዕለ-ነዋይ ክንውኖችን አላካሄዱም። የምርምር ማዕከሎችን አልገነቡም። ስለሆነም አንድ አገር እንደ ህብረተሰብና እንደማህበረሰብ ተከታታይነት ይኖረው ዘንድና፣ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ሳይንሳዊ ባህል እንዲዳብር ታሪካዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ባለመቻላቸው ህዝባችንና አገራችን ተንቀውና ተዳክመው እንዲቀሩ አድርገዋል። የዛሬው የወያኔ አገዛዝም በውጭ ኃይሎች በመደገፍና በመመከር በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው ወጥመድ ውስጥ ከቶናል። በወያኔ አገዛዝ ዘመን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈጠሩት ችግሮች በጣም የተወሳሰቡ ሲሆኑ፣ እነዚህም ፖለቲካዊ፣ ህብረተሰብአዊና ማህበረሰብአዊ፣ ባህላዊ፣ የህሊናና የአካባቢ ቀውሶች ናቸው። የተወሳሰቡና የተደራረቡ ናቸው።፡ ከነዚህ ውስጥ ዋናው ችግር ግን የተፈጠረውን ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና ከዚህ ጋር የተያያዘውን የእሴት መናድ መልክ ማሲያዝ ነው። ይህ ችግር በቀጥታ ከሰዎች ጋር የተያያዘ ሰለሆነ በምን ዐይነት የፖለቲካ ስትራቴጂና ጥበብ ነው በተለይም በኑሮው እየተመቸው የመጣውን የህብረተሰብ ክፍል ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው? የሚለው ነው ማንኛውንም አገር ወዳድ ኃይል የሚያስጨንቀው። ዛሬ እንደምናየው በአገራችን ምድር ውስጥ ድህነት በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል፤ ከተማዎችም መጨናነቂያ ብቻ ሳይሆኑ አቅድ የሌላቸው ሆነዋል፤ በሌላ ወገን ደግሞ በሀብት የናጠጠና ልዩ መኪናዎችን የሚነዳና ከሰፊው ህዝብ በላይ በመሆን ራሱን አግሎ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ተፈጥሯል። ይህም ማለት እዚህ ምዕራብ አውሮፓና የስካንዲኔቪያን አገሮች የማይታይ የአኗኗር ስልት በአገራችን ምድር ተስፋፍቷል። ህብረተሰብአዊ እሴቶች በመበጣጠስ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ተደርጓል። ይህ ሁኔታ በሰፈነበት አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አይቻልም። ምክንያቱም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት ከፍተኛ የሆነ የሞራል ብቃትነት ስለሚያስፈልግ ነው። ካለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል ባልዳበረበትና፣ በተጨማሪም ከተማዎችና መንደሮች በዕቅድና ጥበባዊ በሆነ መልክ ባልተገነቡበት አገር ስለህብረተሰብና ስለማህበረሰብ ማውራት በፍጹም አይቻልም። የልዕልና ወይም የብሄራዊ ነፃነት መጠበቅና አለመጠበቅ የግዴታ ላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ ነው። ስለሆነም አንድ አገር በሁሉም አቅጣጭ የተሟላ ዕድገትና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ባህል ለማዳበር ትችል ዘንድ አንድ የገዢ መደብና ህብረተሰቡ ከፍተኛ ሆነ የሞራል ብቃትነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። በአንድ አገር ውስጥም ታሪክ ሊሰራ የሚችለው ቢያንስ የተወሰነው የህብረተሰብ ከፍል  ሞራላዊ ግዴታ እንዳለበት የተረዳ እንደሆን ብቻ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ወደድንም ጠላንም የወያኔ የተወላገደ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አዳዲስና በቀላሉ ሊፈቱ የማይችሉ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ማለት ይቻላል። ይህም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተቀባይነትን አግኝቷል። በመጀመሪያው እንጀምር። ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለራሱ የከፋፍለህ አገዛዝ ፖሊሲ እንዲያመቸው በማለት በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የብሄረ-ሰብ መብት የሚባለውን ነገር በክልል ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም መሰረት አገሪቱ በዘጠኝ ክልሎች በመከፋፈል፣ በየክልሉ የተወሰነ የህሊና አስተሳሰብ ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን በየክልሉ በሀብት የናጠጡና በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ ስትራቴጂያዊ የመዋዕለ-ነዋይ ክንውን በማካሄድ የስራ መስክ ለመክፈት ያልቻሉ ዋሮ ሎርዶች ወይም አዲስ የኦሊጋርኪ መደቦች ተፈጥረዋል።  ስለሆነም ይህንን የክልል ፖለቲካና የመብት ጥያቄ እንዴት አድርገን ነው መልክ ማስያዝ የምንችለው ? የሚለው ጥያቄ ትልቅ የፖለቲካ ጥበብን የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ስንነሳ ከዶ/ር አቢይና ከአዲሱ ካቢኒያቸው ብዙም መጠበቅ አንችልም። በመሆኑም ይህንን ዐይነቱን የተወሳሰበ የክልል ፖለቲካና በራስ ክልል ውስጥ ብቻ መሽከርከር መፍታት የሚቻለው በተቀነባበረ፣ ኢንስቲቱሽናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰብአዊና በዕውቀት አኳያ በሚካሄድ በተቀነባበረ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። ይህንን ቀስ በቀስ ተግባራዊ ለማድረግ ከሁሉም ብሄረ-ሰቦች የተውጣጡ ወጣቶች ሁለንታዊ በሆነ መልክ ሊሰለጥኑ የሚችሉበት ኢንስቲቱሽን በየክልሉ ዋና ከተማዎች መቋቋም አለባቸው። ከዚህ ተኮትኩተው የሚወጡት ወጣቶች በወረዳ፣ በአውራጃና በክልል ደረጃ የመሪነትን ቦታ በመውሰድና እዚያው ልምድን በማካበት እንደየችሎታቸው በማዕከል ደረጃ አዲሱ የገዢ መደብ የሚሆኑበት ሁኔታ ይመቻቻል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ወያኔ የተከተለውን የክልል ፖሊሲ ዝምብለን በጭፍን በልዑላዊነት ስም ማጠፍ አንችልም። ይህ ጉዳይ የፖለቲካ ጥያቄ እንደመሆኑ መጠን መፈታትም የሚችለው ጥበብ በተሞላበት ፖለቲካና ከዚህ ጋር በተያያዘ የመዋዕለ-ነዋይ ፖሊስ አማካይነት ብቻ ነው። የስራ መስኮች ሲፈጠሩ፣ ሰፊው ህዝብ የሚተዳደርበት ተከታታይ የወር ገቢ ሲያገኝ፣ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ሲሟሉለት፣ ከተማዎችና መንደሮች በዕቅድ ሲገነቡና፣ ህዝቡም አዲሱን ኖሮ ሲለምደውና ተጠቃሚም ሲሆን፣ በዚያው መጠንም የልዑላዊነትና የአገር ወዳድነት ጥያቄዎች ተመለሱ ማለት ነው። ይህንን በሚመለከት አፍሪካን ፕሬዲካመንትስ(African Predicaments and the method of solving them effectively) በሚለው መጽሀፌ ውስጥ ሰፋ ባለመልክ ያቀረብኩትን ሀታታና የመፍትሄ ጉዳይ መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል።

ወደ ሌሎች ጉዳዮች ስንመጣም ወደድንም ጠላንም በመሬትና በተቀረው የሀብት ይዞታ  አማካይነት አዲስ የሆነ የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ግኑኝነት ተፈጥሯል። አገዛዙ በወሰደው የግብረ-ወጥ ፖሊሲ አማካይነት በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከመሬታቸውና ከቤታቸው በመፈናቀል ለድህነት ተዳርገዋል። መጠለያ አጥተዋል። ይህንን የተወሳሰበና የሀብት ዘራፋና በጥቂት ሰዎች እጅ መከማቸትን እንዴት አድርገን ነው መፍታት የምንችለው ?  እነዚህና ሌሎች ማህብረሰብአዊና ሰፊውን ህዝብ ወደድህነትና ወደድቀት የገፈተሩትን ሁኔታዎች በምን መልክ በማረም ነው ህብረተሰብአዊ መረጋጋት መፍጠር የምንችለው ?  እንደተመለከትነውና ልምድም እንዳስተማረን ዝም ብሎ የሚነጠቅ ሀብት የባሰውኑ ህብረተሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ነው የሚከተን። ስለሆነም በሶስዮሎጂና በሀብት ክፍፍል የሰለጠኑና ሁለንታዊ ዕውቀት ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ በቡድን የተደራጁ ሁኔታውን በማጥናት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መፍትሄ ማቅረብ መቻል አለባቸው። ከዚህና ከሌሎች የተወሳሰቡ ሁኔታዎች ስንነሳ እኛ የምንመኘውና በምድር ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አንድ ላይ የሚጓዙ አይደሉም። ሰልሆነም ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቁና በማስተማርና በማስረዳት፣ እንዲሁም በመወያየትና ከዚህ በሚፈልቀው በደንብ በተጠናቀረ ሳይንሳዊ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር መፍታት የሚቻለው። መስረታዊ ለውጥም ከመቅጽበት የሚመጣ ሳይሆን ከረጂም ጊዜ በኋላ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህ በራሱ ደግሞ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ምሁራንን የማያቋርጥ ተሳትፎና ትግል ይጠይቃል።

 

ዶ/ር አቢይ እነዚህን ችግሮች ብቻውን ሊፈታቸው ይችላል ወይ ?

በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የአንድ አገር ችግር በአንድ ጊዜ የሚፈታ አይደለም። የአንድ ህብረተሰብ ችግር በክንዋኔ ወይም በሂደት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። ሌላው ዋና መሰረተ-ሃሳብ የአንድ አገር ችግር በአንድ ሰው ብቻ የተፈታበት ጊዜ የለም። በተለይም የምዕራብ አውሮፓን የካፒታሊዝም ዕድገትና የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ስንመለከት ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ሰዓሊዎች፣ የክላሲካል ሙዚቃ ስዎች፣ የከተማ አገነባብና የቤት አውቃቀር አጥኒዎችና ባለሙያተኞች፣ ወዘተ…. ወዘተ በመካፈልና ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሆን ብቻ ነው ቀስ በቀስ ለውጥን ማምጣት የቻሉት። ከዚህም በላይ በጊዜው በተለይም የመሬትን ሀብት የሚቆጣጠረው የህብረተሰብ ክፍል ለውጥ እንዳይኖር ከፍተኛ ትግል የሚያደርግ ስለነበር የሊበራል አስተሳሰብ ያላቸውና የቴክኖሎጂ ዕድገትን አስፈላጊነት የተገነዘቡ ምሁራን አንድ ላይ በመሰባሰብ ነው በተለይም በተገለጸላቸው ሞናርኪዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖና ግፊት በማድረግ ቀስ በቀስ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደረጉት። ለመሰረታዊ ለውጥ ደግሞ የግዴታ ሁለንታዊና ጭንቅላትን የሚያድስ ትምህርት ተግባራዊ መሆን ነበረበት። በዚህም ምክንያት ነው እንደጀርመን የመሳሰሉት አገሮች በአንድና በሁለት ትውልድ ጊዜ ውስጥ ሳይንቲስቶችን፣ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎችን፣ ፈላስፋዎችንና የማቲማቲክስ ምሁራንን ለማፍልቅ የቻሉት። ሪማን፣ ጋውስና አነስታይን የዚህ ዐይነቱ አጠቃላይና ስር-ነቀል የትምህርት አስጣጥ ዘዴ ውጤቶች ናቸው።

የብዙዎቻቸን ችግር ስለለውጥ ወይም ስለመሰረታዊ ለውጥ በምናውራበት ጊዜ ስለምን እንደምናውራ በግልጽ የምናስቀምጠው ነገር የለም። አንድ በጭንቅላታችን ውስጥ የሳልነው ስዕል ስለሌና፣ ይህንንም በትንታኔ ደረጃ በረጃ ስላላስቀመጥን ዝምብለን ስለለውጥ ብቻ እናውራለን። በተለይም አገራችን እንደአገር በፀና መሰረት እንድትገነባ ዘንድ እንደሞዴል አድረገን የምንወስደው አገርና ህብረተሰብ ስለሌለ አገሪቱ ለውጥ ያስፈልጋታል እያልን ብቻ እናወራለን። ከአገራችንም ሆነ ከሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተወሳሰቡ ችግሮች ስንነሳ የብዙዎቻችን ችግር የኛ ዕድልና ምኞት በኛ የሚወሰን ሳይሆን ወደደንም ጠላንም በካፒታሊስት አገሮችና እነሱ በፈጠሩት እንስቲቱሽኖች አማካይነት ብቻ ነው። ስለሆነም የፈለግነውን ያህል መሰረታዊ ለውጥ መኖር አለበት እያልን ብንጮህም መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መዳፍ ስርና እሱ ከፈጠራቸው ኢንስቲቲሽኖች ውጭ ወጥተን ነፃ አገር ልንገነባ በፍጹም አንችልም። ይህንን የምልበት ምክንያት ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን እኛ ምሁሮች የምንባል የኢትዮጵያን ህዝብ ዕድል በአሜሪካን መነጽር ብቻ ስለምናየውና፣ የተለያየ ምክንያት በመፍጠር ለዕውነተኛ ዕድገት የሚደረገውን ትግል ስለምናጨናግፍና ስለምናሳስት ነው። ይህንን በሚመለከት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ዕድገትን ሳይሆን ፀረ-ዕድገትንና የተመሰጣጠረ ብዝበዛንና ጭቆናን የሚያስፋፉና የሚያጠናክሩ ግለሰቦች በየቦታው አሰማርቷል።፡

የብዙዎቻችን የለውጥ ፈላጊዎች ችግር በተለይም በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠረውን ፓለቲካዊና ህብረተሰብአዊ ቀውስ ወያኔ ብቻ የፈጠረው ችግር  አድርገን መመልከታችን ነው። ከዚህ ስንነሳ የኢኮኖሚን ጥያቄ በሚመለከት የወያኔ አገዛዝ እስከዛሬ ድረስ በተከተለውና በሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ አንዳችም የጠራ አመለካከት የለንም። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት ወያኔ እስከዛሬ ድረስ የሚያካሄደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአብዮታዊ ዲምክራሲ ወይም የሶሻሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚል ነው። በተለይም በዚህ ላይ የጠራ አቁም ሳይኖረንና፣ በተጨማሪም በተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች ላይ ግልጽ አመለካከት ሳይኖረን እንዴት አድርገን ነው አገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋታል እያልን መጻፍ የምንችለውና የምንወተውተው ?

ከዚህ በመነሳት ግልጽ የሆነ ህብረተሰብአዊ አውቃቀርና አጠቃላይ የሆነ የአገር አገነባብ ስልትና የሀብት ፈጠራ ዘዴ እስከሌለን ድረስ ዝም ብለን በጭፍኑ ስለስር-ነቀል ለውጥና  ስለ ልዕልና ጉዳይ በፍጹም ማውራት አንችልም። በዚህና በአያሌ አንድን ህብረተሰብ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ግልጽ የሆነ አመለካከት ሲኖረን ብቻ ነው ዛሬ የተፈጠረውን መጠነኛ የሆነ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ መገምገምና የራሳችንን አስተያየት መሰንዘር የምንችለው። እንዲያው በደፈናው የምንሰነዝራቸው ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው አነጋገሮች የመጨረሻ መጨረሻ ኃይልን የሚበታትኑና የኢትዮጵያን ህዝብ ህልም የሚያጨልሙ ናቸው።

ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ወደ ዶ/ር አቢይ ጋ ልምጣ። በአንዳንዶች የሚሰነዘረው አስተያየት ዶ/ር አቢይ ስርዓቱ የፈጠረው ወይም ያሳደገው ስለሆነ የወያኔን ፖሊሲ ከማካሄድና የእነሱን ዕድሜ ከማራዘም በስተቀር ሌላ ተግባር ሊኖረው አይችልም የሚል ነው። በመሰረቱ አንድ ግለሰብ በአንድ ስርዓት ውስጥ ስለአደገ የግዴታ በዚያ ውስጥ ሲስፋፉ የነበሩ እምነቶችን ወይም ርዕዮተ-ዓለሞችን ሙሉ በሙሉ በመቀበል ሊያራግባቸው አይችልም። እንኳን በአንድ ስርዓት ውስጥ ቀርቶ ከአንድ ማህጸን የተወለዱና ተመሳሳይ እንክብካቤ የተደረገላቸውና ተመሳሳይ ምግብ በልተው ያደጉ ልጆች የኋላ ኋላ በአስተሳሰባቸው ተመሳሳይ አቋም ሊይዙ አይችሉም። አንዱ የቀኝ ዝንባሌ ሲይዝ፣ ሌላው ደግሞ የግራ አቋም በመያዝ  ለሰብአዊ መብትና ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚታገል ይሆናል። በሌላ አነጋገር በአንድ ስርዓት ውስጥ ማደግና በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በጭፍን አስተሳሰብ (Indoctrization) በመኮትኮት እሱን መስበክና ሌላው እንዲቀበለው በማድረግ መሀከል ትልቅ ልዩነት አለ። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ የቻለው እግዚአብሄር አንዳንድ ግለሰቦችን  ከላይ ለውጥ እንዲያመጡ ስለወረወራቸው ሳይሆን ከዚያው የህብረተሰብ አካል ውስጥ የፈለቁ ናቸው። ፕላቶንና አርስቲቶለስ የአሪስቶክራሲው መደብ ልጆች ነበሩ። ከአሪስቶክራሲው መደብ በመፍለቃቸው ግን የአሪስቶክራሲውን መደብ ወግ-አጥባቂነት የራሳቸው በማደረግ መስበክና ማስተማር አልጀመሩም። በመደነቅ ዓለም ውስጥ በመግባት የተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ምንነትና ባህርይ በማጥናት ልዩ የሆነ ጥበባዊ አስተሳሰብ ማዳበር ችለዋል።  ለሰው ልጅ ዕድገትና ስልጣኔ ምን ምን ነገሮች እንዳበረከቱ አብዛኛዎቻችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። እነሱም ሆነ ሶክራተስና በኋላ የተነሱት ፈላስፎች በፈጠሩት ፍልስፍናና ሳይንስ መሰረት ነው የሰው ልጅ ከጨለማ ዓለም ውስጥ ወጥቶ ብርሃንን ማየት የቻለው። የኋላ ኋላ የተነሱት የሳይንስና የፍልስፍና እንዲሁም የማቲማቲክስና የኢኮኖሚክስ ምሁራንና ፈጣሪዎች ወላጆቻቸው የግል አስተማሪዎች እየቀጠሩላቸው ባስተማሯቸው ታላላቅ ምሁራን አማካይነት ነው በዓለም ላይ ስልጣኔ ሊስፋፋ የቻለው። ወደድንም ጠላንም ያለው ሀቅ ይህ ነው። ከዚህ ስንነሳ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ወይም አካባቢ መወለድና ማደግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጭንቅላትን በሚያጨልም ባህል ወይም ርዕዮተ-ዓለም ተኮትኮቶ ማደግና እሱን የሙጥኝ ብሎ በመያዝ የዕድገት ፀር በመሆን መሀከል የሰማይና የምድርን ያህል ዕርቀት አለ። ስለሆነም በአንድ በኩል በወያኔዎች፣ ስብሃት ነጋ፣ አቦ ፀሀይ፣ በረከት ሰመዖን፣ ስዩም መስፍን፣ ደብረ ጽዮንና አርከበና እንዲሁም ሌሎች የወያኔ ሰይጣኖችና የተንኮል ፋብሪካዎች፣  በሌላ ወገን ደግሞ  በዶ/ር አቢይና አቶ ለማ መገርሳ መሀከል የሰማይንና የመሬትን ያህል የርቀት ልዩነት እንዳለ መገንዘብ እንችላለን። ስለሆነም ዶ/ር አብይን ትግሉን እንደሚያደናቅፍ ግለሰብ አድርጎ መውሰዱ ስህተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ አባባል ነው። ከዛሬውም የተወሳሰበ የአገዛዝ መዋቅር በመነሳት ከሱም ብዙም ልንጠብቅ ባንችልም፣ በሌላ ወገን ግን የተፈጠረወን አዲስ የፖለቲካ ሁኔታ በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ማየቱ ትልቅ ስህተት መስራት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው።

ስለሆነም የዶ/ር አቢይ መመረጥ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ከፍቷል ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአገሪቱ የተወሳሰቡ ችግሮችን የተገነዘበ ይመስላል። የፓለቲካ ባህል ማጣት፣ ደጋግሞ የሚያነሳው የዕልከኝነት ባህል፣ ተከታታይነት ያለው ታሪክ ለመስራት ያለመቻልና፣ አዳዲስ የሚፈጠረው ትውልድ ወይም የፖለቲካ ስልጣን ላይ የሚቀመጥ የቀድሞውን ታሪክ በማንኳሰስና የተሰሩ ስራዎችን ሁሉ በማፍረስ እንደአዲስ መጀመሩና ሌሎች ጉዳዮችን እያነሳ ለማወያየት ሞክሯል። እሱን ከቀደሙት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስተሮች በተሻለ መጠን ራሱን በደንብ ለመግለጽና አገሪቱም ምን እንደሚያስፈልጋት በተቻለ መጠን ረጋ ብሎ ለማስቀመጥ የሚሞክርና የሚጥር ነው። ሰሞኑን በየቦታው እየተዘዋወረ የሚያደርጋቸው ገለጻዎችና ከህዝብ ጋር መወያየትና የእነሱንም ቅሬታዎች መስማትና በተቻለ መጠንም ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ መሞከር በህዝብ ዘንድ ተደማጭነትን አስገኝቶለታል። ህዝቡም መተንፈስ ችሏል። በሚያቀርባቸው ጥያቄዎችና በሚሰነዝራቸው አስተያየቶች ህዝባችን የቱን ያህል የነቃ መሆኑና ለለውጥ ያለውንም ፍላጎት አረጋግጧል።፡ ከዚህ ባሻገር ሁለቱም፣ አቶ ለማም ሆነ ዶ/ር አቢይ ከበስተጀርባቸው ምንም የሚያስቡት ተንኮል ነገር እንደሌለ ገጽታቸውን ለሚያነብ ሊገነዘብ ይችላል። ስለዚህም እነሱን የአገዛዙ አፈቀላጤዎች ወይም ትግሉን የሚያጨናግፉ ኃይሎች አድርጎ መመልከቱ ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛ አባባልም ነው።

ያለው ችግርና ዶ/ር አቢይ በቀላሉ ሊፈታቸው የማይችላቸው ነገሮች የመንግስት አወቃቀር ጉዳይ ነው። ወያኔ በመንግስቱ መኪና አማካይነት ነው ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን የቻለውና በሀብት መደለብ የበቃው። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር ዕድገት፣ ሰላምና መረጋጋት የግዴታ የመንግስት መኪና ጉዳይ መልስ ማግኘት አለበት። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ባለፉት ሰላሳ ዐመታት በየአራት ዐመቱ ምርጫዎች ተካሄደው አሁንም ቢሆን ህዝቦች በነፃነት እጦትና በድህነት የሚማቅቁት ቀድሞ የተዘረጋው ጭቆናዊ የመንግስት አወቃቀር ጥገናዊ ለውጥ ባለማግኘቱና ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ሊኖረው ባለመቻሉ ነው። ከዚህም በላይ የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገር ኢኮኖሚዎች ውስጠ-ኃይሉ ደካማ ስለሆነ በጣም የነቁና ተራማጅ የሆኑ የህብረተሰብ ኃይሎችን የመፍጠር ኃይሉ በጣም ደካማ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ሳይንቲስቶችን፣ ፈላስፋዎችን፣ የቴክኖሎጂና የህብረተሰብ ሳይንስ አዋቂዎችን በማፍለቅ ስርዓትን ለመጋፈጥና ለዕድገት አመቺ ሁኔታን መፍጠር የማይቻልበት ሁኔታ በየአገሩ ተስፋፍቷል። በአገራችንም ያለው ትልቁ ችግር ይህ ነው። ሰፋ ያለ ምሁራዊ መሰረትና የነቃ ኃይል ስለሌለ ከአገዛዙ ባሻገር የተሻለና ለለውጥ የሚያመች ሁለንታዊ ፖሊሲ ለማፍለቅ አይቻልም።

ስለሆነም የመንግስቱን መኪና ጥገናዊ ለውጥ በሆነ መልክ መለወጥና ወደታች በመሄድ በኢኮኖሚ መስክ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ከተፈለገ በአንድ ግለሰብ ወይም በሁለት ሰዎች ላይ የሚጣል ሳይሆን ሁላችንም ዕውነተኛ ለውጥ ፈላጊዎች ከሆን የግዴታ እንደነ ዶ/ር አቢይ የመሳሰሉቱን የነቁና ውስጠ-ኃይል ያላቸውን ግለሰቦች ማበረታታት አስፈላጊ ይመስለኛል። ድርጊታቸውን ክሪቲካል በሆነ መንገድ እየተከታተሉ የተሻለ ሃሳብ በመሰንዘር ለውጥ እንዲመጣ አብረን በጋራ መታገል ብንታገል ህዝባችንን አገዝነው ማለት ነው። ስለሆነም በምናድረገው የተቀነባበረ ትግል የወያኔን የጨለማና ፋሺሽታዊ አገዛዝ በተቻለ መጠን ከህዝቡ እንዲነጠል(neutralaize) ማድረግ አለብን። ዶ/ር አቢይን በዚህ መልክ መደገፍ ማለትም ከኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ መቆምና ለተሻለ ስርዓት መታገልም እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። እሱ ደጋግሞ እንደሚያነሳው በመደመር ወይም በመተባበር እንጂ በመነጣጠልና ርስ በርስ በመናቆር አይደለም ለውጥ ማምጣት የሚቻለው። ህብረተሰብአዊ ለውጥም እንዲመጣ ከተፈለገ የግዴታ በስልጣን ውስጥ መካተት የለብንም። የየራሳችንን የጥናት ክበብ በመመስረትና ፕራክቲካል ስራዎችን በመስራት የለውጥ አጋዦች መሆን እንችላለን። በዚህ መሰረት በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመፍጠርና ሃሳቦች በማፍለቅ እንደህ ዐይነት ብሩህ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ሲነሱ እነሱን መደገፍና ማበረታታት ያስፈልገል። የሆነ ያልሆነ ምክንያት እየፈጠርን ወይም ትንሽ የአነጋገር ስህተት ሲከሰት አቃቂር እያወጣን የምናሽሟጣጥ ወይም የምንጠረጥር ከሆነ ወይም ይቅርታ ይጠይቅ የምንል ከሆነ ስራ እንዳይሰራ ነው እንቅፋት የምንሆነው። መሰረታዊ የሆነ የፖሊሲ ስህተት እስካልተሰራ ድረስና እሱን ተገንዝቦ እርማት ለማድረግ ዝግጁ እስካልተሆነ ድረስ  የዚያን ጊዜ ቅሬታችንን ማሰማት እንችላለን። በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ፖለቲከኞች አንዳንድ ንግግር ከማድረጋቸው ወይም ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት መጀመሪያውኑ ከአማካሪዎቻቸው ጋር አይመካከሩም። ፖለቲከኞችም በሪህቶሪክ አይሰለጥኑም። የፖለቲካ አማካሪዎች የሚባሉትም ራሳቸው የጠለቀ ዕውቀት ስለማይኖራቸው ግንዛቤን የሚሰጥ ምክር ሊለግሱ አይችሉም። በዚህ ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የአገራችን ፖለቲከኛ ነን ባዮች የሚናገሩት ዝምብለው ነው። ከዚህ ሁኔታ ስነሳ ዶ/ር አቢይ የተሻለ አቀራረብ ያለው ይመስለኛል። ወደፊት በስህተትና በልምምድ የሚሻሻሉ ነገሮች አሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው የኛ የቀና አመለካከትና ሳይንሳዊ ግንዛቤና ምራቅ የዋጠ ትንታኔ ሲታከልበት ብቻ ነው። ስለሆነም ነገሮችን በጥሞና መከታተልና መረዳዳት፣ እንዲሁም በጎደለው ላይ እየሞሉ ወደፊት መራመዱ አማራጭ የሌለው አካሄድ ነው እላለሁ። ከዚህ ስነሳ የዶ/ር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስተር መሆን እንደ አንድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በመታየት የተወሳሰበውን የጋራ ችግር በጋራ ለመፍታት መጣር የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሌላ አማራጭ አለ ከተባለም መሰንዘሩ ክፋት የለውም። ዋናው ቁም ነገር ሁላችንንም ወደ ግብግብና ጭቅጭቅ ውስጥ የሚያሰገባን መሆን የለበትም። ከዚህ በመነሳት ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ  የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ።

1ኛ) የመንግስቱ መኪና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልክ መዋቀር አለበት። በተለይም የፀጥታው ክፍል እንዳለ  መዘጋት አለበት። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተዘረጉ የፀጥታ መዋቅሮች ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚታገሉ ኃይሎችን የሚያፍኑና የሚገድሉ ስለሆነ ለገዢው መደብ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች እንጂ ህዝባዊ ባህርይ በፍጹም የላቸውም። በስለላ የሚሰለጥኑትም ከወጭ የስለላ ድርጅቶች ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያላቸው ሲሆኑ፣ አንድ መንግስት መስራት ያለበትን  ነገር እንዳይሰራና በመሰረታዊ የአገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ እንዳያተኩር ያግዳሉ። በዚህም የተነሳ የህዝብ ሀብት በማይሆን መስክ ላይ እየፈሰሰ ራሱ ህዝቡ የራሱን ጨቋኝ ኃይል ያደልባል። የሚገድሉትንና የሚያሰቃዩትን ይቀልባል። ፀጥታን ለማስጠበቅ በሚል ስም የሰው ልጅ ህይወት ምን እንደሆነ ቅንጣትም የማይሰማቸው አግአዚ የሚባል የፋሽሽቶች ቅልብ ጨፍጫፊ ኃይል በማዘጋጀትና በማሰልጠን ስንትና ስንት ዕድል የሚጠብቀውን ወጣት እያነጣጠረ እንዲገድል ያደርጋሉ። በእኔ ዕምነት እንደዚህ ዐይነት ፋሺሽታዊ ኃይሎች ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት አለባቸው። በአግአዚ ስር ለጭፍጨፋ የተመለመሉ ምስኪን ወንድሞቻቸን በመንገድ ስራና ድልድይ ግንባታና እነዚህን በመሳሰሉት ላይ በመሰማራት ህብረተሰብአዊ ሀብት ፈጣሪዎች መሆን አለባቸው። ባጭሩ ለአንድ አገር የአገር ውስጥ ሚንስተርና ከሱ ስር የሚተዳደሩ የፖሊስ ኃይሎች ፀጥታን ለማስከበር በቂ ናቸው። ከዚያ ውጭ ያለው ትርፍ ነው።

2ኛ) በአገራችን ምድር የተቀላጠፈ ስራ ለመስራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት ለማግኘት የኢንስቲቱሽን የጥገና ለውጥ ማድረግና በየቦታውም አዳዲስ ኢንስቲቱሽኖችን ማቋቋም አስፈላጊ ነው። ብቃትነት ባላቸው ኢንስቲቱሽኖች አማካይነት ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ ያለን የሰውን ኃይልና የተፍጥሮን ሀብት በማንቀሳቀስ ዕድገትን ማምጣት የሚቻለው። ስለሆነም አዲስ ወጣት ትውልድ በየፊልዱ በማሰልጠን በየኢንስቲቱሽኖች ውስጥ በማካተት እያረጀ የሚመጣውን ቢሮክራሲ መተካት አለባቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በየቦታው ማዘጋጃ ቤቶች ማቋቋምና በሰለጠኑ ሰዎች እንዲመሩ ማድርገ ዕድገትን ያፋጥናል። በዚህ መሰረት የከተማ ዕቅድ አውጭዎች፣ እርኪቴክቸሮች፣ መሃንዲሶችና ኢንጅነሮች፣ የህክምና ባለሙያዎችንና ሌሎችን በማሰልጠን ኢንስቲቱሽኖች ብቃትነት ባለው መሰረት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

3ኛ) ዲሞክራሲያዊ ነፃነቶችን ማክበርና ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ የሙያ ድርጅቶች ህጋዊ በሆነ መልክ በማህበር እንዲቋቋሙ መፍቀድ አስፈላጊ ነው። ከዚህም በሻገር የተለያዩ የሲቪል ማህበራት የሚፈጠሩበትንና የሚቋቋሙበትን ህጋዊ ሁኔታዎች ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

4ኛ) በእኔ ዕምነት የፓርቲዎች ጋጋታ ወይም የመደብለ ፓርቲ መኖር የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር በፍጹም ሊፈታው አይችልም። ከአገራችንና ከብዙ የአፍሪካ አገሮች ልምድ ስንነሳ አብዛኛዎች ለስልጣን ብቻ የሚታገሉ ፓርቲዎች የፍልስፍና፣ የቲዎሪና የሳይንስ መሰረት የላቸውም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድ  አገር ከታች ወደ ላይ ጥበባዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደሚገነባ በፍጹም ግንዛቤ አይኖራቸውም። ልምድም እንዳስተማረን ምርጫን አሸንፈው ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉ ፓርቲዎች ወይም አንድ ፓርቲ የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው ወይም የዓለም አቀፍ የገንዝብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚያቀርቡለትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የባሰውኑ ድህነትን ያስፋፋል፤ የህዝቡን ውስጣዊ ኃይል በማዳከም አገር እንዲበታተን አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ስለሆነም በተለያዩ ፓርቲዎች አማካይነት በአገራችንም ሆነ በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታትና እንደ አንድ ህብረ-ብሄርና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የግዴታ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ሰዎች፣ ፈላስፋዎች የሶስዮሎጂ ምሁራን፣ በአርኪቴክቸር ሙያ የሰለጠኑና እነዚህን የመሳሰሉት የመንግስቱን መኪና በመቆጣጠር አገር ማስተዳደር አለባቸው። ይህ ሁኔታ ከ30-50 ዓመት ተከታታይነት እንዲኖረው ተተኪ የአገር መሬዎች በዚህ መልክ እየሰለጠኑ ኃላፊነትን የሚቀበሉበት ሁኔታ መዘጋጀት አለብት።

ከዚህ ስንነሳ ስልጣንን የሚጨብጡና አገርን የሚያስተዳድሩ የግዴታ አገር ውስጥ መሰልጠን ያለባቸው ናቸው። ክታች ወደላይ ከትናንሽና እስከዋና ከተማዎች ድርሰና ከዚያም አልፈው በክፍለ-ሀገር ደረጃ በተመደቡበት ቦታ ሁለ-ገብ ዕድገት ካመጡና፣ ከተማዎችንና መንደሮችን ጥበባዊ በሆነ መንገድ ከገነቡ በአገር አቀፍ ደረጃም አንድን አገር ለማስተዳደር ይችላሉ ማለት ነው። አንድ ሰው የዶክትሬት ዲግሪ ስላለው ወይም ደግሞ በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽን ውስጥ ስለሰራ ከፍተኛ ስልጣን ከተሰጠው እንደዚህ ዕይነቱ ሰው ወይም ሰዎች አንድን አገር ጥበባዊ በሆነ መልክ ሊገነቡ በፍጹም አይችሉም። በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ በመገንባት አንድን አገር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ማድረግ በፍጹም አይችሉም። ከጋና በፕሬዚደንት ኩፉር(John Kufuor) ዘመን፣ በላይቤሪያ ደግሞ ከሚስ ኤለን ጆንሰን(Ellen Johnson) የግዛት ዘመን የምንማረው ሀቅ እነዚህ መሬዎች ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት እንዳልቻሉ ነው። የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው ታዛዥ በመሆናቸው ብቻ ከበሬታንና ሽልማትን ያገኙ ናቸው። ስለዚህም ማትኮር ያለብን ከውስጥ ውስጠ-ኃይል ያላቸው አገር ወዳድ ኢትዮጵያንን ማፍራት ነው።

5ኛ) የኢኮኖሚን ጉዳይ በሚመለከት በተለይም የመሬት ጥያቄን አስመልክቶ ገበሬው በይዞታ የሚያርሰውና የሚያስተዳድረው መሬት እንደችሎታውና እንደቤተሰቡ ቁጥር ማግኘት አለበት። በህገ-ወጥ ትላልቅ እርሻዎችን ለማስፋፋት እየተባለ መሬቱን የተነጠቀው ገበሬ መሬቱን ማግኘትና ቀዬው እንዲመለስለት ማድረግ ያስፈልጋል። በዚያው መጠንም  ወደ ውጭ ለመላክ ብቻ የሚታረሱ የእርሻ ተግባሮች መቆም አለባቸው።፡

ሰለሆነም ትናንሽና ማዕከለኛ ገበሬውን የሚደግፍና የሚደጉም ፖሊሲ በማውጣት ልዩ ልዩ ሰብሎች እንዲመረቱ በማድረግ አገሪቱ በእርሻ ምርት እራሷን እንድትችል ማድረግ ያስፈልጋል። አንድ አገር በምግብ እራሷን ካልቻለች በፍጹም ልታድግ አትችልም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት 27 ዓመታት የአገራችን ባህላዊ ዘር ከውጭ በሚመጣ በመተካቱ አገሪቱ በብዙ መንገዶች በውጭ ጥገኛ ሆናለች። ከውጭ የሚመጡ ዘሮች ደግሞ ካለማዳበሪያና ካለተባይ ማጥፊያ ስለማይበቅሉ ገበሬው በብዙ መልክ ጥገኛ ሊሆን በቅቷል። የአገራችንንም የዳየት ስይስተም በመለወጡ ብዙ ሰው ለዘመናዊ በሽታዎች ተጋልጧል። የኩላሊትና የስኳር በሽታዎች ተስፋፍተዋል። በተለይም ከውጭ በሚመጣ የፓልም ዘይት የተነሳ ብዙ ሰው በኩላሊት በሽታ እየተሰቃየና ኩላሊቱንም እያጣ ነው።

ይህንን አስመልክቶ አገራችን ውስጥ ለዘይት የሚያገለግሉ እንደሰሊጥ፣ ተልባ፣ ኑግና ሱፍ እየተመረቱ እነሱን እየጨመቁና እያጣሩ ለህዝባችን ዘይት ማቅረብ ሲገባ እነዚህ የሰብል ዐይነቶች ዶላር ለማግኘት ሲባል እንዳለ እስከነነፍሳቸው ይላካሉ። የወያኔ መንግስትና ካድሬዎቹ በዚህ መልክ ሀብትን ሲቆጣጠሩና ሲደልቡ፣ በዚያው መጠንም ህዝባችንን ለበሽታ እያጋለጡትና እንደኩላሊት የመሳሰሉትን አስፈላጊ የሰውነት ክፍሎችን እንዲያጣ እያደረጉት ነው።  በዚህ መልክ የወያኔ የእርሻ ፖሊሲ ለኢንዱስትሪ አገሮች የጥሬ ሀብት እንዲያቀርብ ሆኖ የተዋቀረ ፖሊሲ ነው። ድህነትን የሚያስፋፋ የእርሻ ፖሊሲ ነው። ወያኔና ግብረአበሮች በህዝባችንና በአገራችን ላይ ትልቅ ወንጀል የሰሩና እየሰሩ ለመሆናቸው ከዚህ ብቻ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል።

ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ የጋሻ መሬቶች ለአበባ ተከላ እንዲውሉ በማድረግ አካባቢ እየወደመና የሰው ጤንነት  እየተቃወሰ ነው። እንደሚታወቀው አበባ የኢኮኖሚ ቫልዩ የለውም። የጥሬ ሀብት በመሆን በፋብሪካ ውስጥ የሚፈበረክ አይደለም። ስለሆነም በዚህ መልክ ለእርሻ መሬት የሚውለውን ማሳ እየቀሙ ለአበባ ተከላ ማዋል ከፍተኛ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። የባህል ውድመት ማድረስና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ ማገድ ነው። ይህ አደገኛ ተግባር እንዲቆም ማድረግና አፈሩን እየመረመሩ ልዩ ልዩ ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች የሚዘሩበትንና የሚበቅሉበትን ሁኔታ ማዘጋጀት የአዲሱ አገዛዝ፣ በተለይም የእርሻ ሚኒስተሩ ሃላፊነትና ሞራላዊ ግዴታ ነው። እንደሚታወቀው የውጭ ከበርቴዎች በዚህም መስክ ሆነ በሌሎች መስኮች የሚያካሂዱት የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ በመሰረቱ ዕድገትን አያመጣም። የውጭ ከበርቴዎችም ዋና ዓላማ ርካሽ ጉልበትን ተጠቅሞ ትርፍ ለማካበት ስለሆነ ዕውነተኛ በሳይንስ ላይ የተመሰረተና ሁለ-ገብ የሆነ ዕድገትን አያመጡም። ቤቶችን፣ ትምህርትቤቶችን፣ የባህል ማዕከሎችንና ክሊኒኮችን በመገንባትና በማስፋፋት ለአንድ አገር ሁለ-ገብ ዕድገት በፍጹም አስተዋፅዖ አያደርጉም። ስለሆነም በተለይም ማንኛውም የውጭ ከበርቴ በእርሻ መስኩ ላይ እንዳይሳተፍ በህግ መከልከል ያስፈልጋል። ይህንን የማያደርግ መንግስት ታሪካዊ ግዴታውን በፍጹም ሊወጣ አይችልም ማለት ነው።

ከዚህ ስንነሳ የእርሻው መስክ ልዩ አትኩሮ የሚያስፈልገውና ልዩ ልዩ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች አንዲሁም አትክልቶች እንዲተከሉና እንዲስፋፉ ማድረግ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው።  የእርሻው መስክ ከማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲያያዝ በማድረግ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ለአንድ አገር ዕድገት የውጭ ገበያ ሳይሆን በመጀመሪያ ደረጃ የአገር ውስጥ ገበያ ማደግና መስፋፋት ነው ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ መሰረት።

6ኛ) በአገራችን ሰሞኑን የሚወራው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ጉዳይ ነው። በዚህም የተነሳ ብዙ ኢንቬስተሮች የውጭ ምንዛሪ እንደልብ ለማግኘት እንዳልቻሉ በየጊዜው እሮሮ ያሰማሉ። የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚመነጨው አገሪቱ አሁንም የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት በጥቂት የእርሻ ምርት ውጤቶች ላይ፣ በተለይም በቡና ላይ በመመካቷ ነው። አገራችን ቡናን እያመረተች ወደ ውጭ ስትልክ ከመቶ ዐመት በላይ ሊሆነው ነው። ባለፉት ስድሳ ዐመታት የተለያዩ የአገራችን አገዛዞች የዚህን አሉታዊ ጎን በማጥናት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ ሊያደርጉ በፍጹም አልቻሉም። በተለይም ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ትዕዛዝ በተቅዋም የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Structural Adjustment Policy) አማካይነት ቁጥራቸው የማይታወቁ የከረንሲ ቅነሳ(Devalutaion) ፖሊሲ አካሂዷል። በፖሊሲው አውጭዎች ዕምነትም አንድ ደካማ አገር የአገሯን ከረንሲ ከዶላር ጋር ሲወዳደር በተወሰነ ፐርሰንት ብትቀንስ ወደ ውጭ የምትልከው የጥሬ ሀብት በብዛት ገዢ ያገኛል የሚል ነው። ይህ ፖሊሲ በተደጋጋሚ ተግባራዊ ቢሆንም ኢትዮጵያ በቡናና በሌሎች ወደ ውጭ በሚላኩ ሰብሎች ሽያጭ የተነሳ ብዙ የውጭ ከረንሲ ልታገኝ አልቻለችም። የንግድ ሚዛኑም ከመሻሻል ይልቅ በየጊዜው እየተዛባና ወደ ውስጥ ደግሞ የዋጋ መወደድን እያስከተለ ነው። ከዚህ ዐይነቱ የዙሪያ ጥምጥም ለመውጣት በመጀመሪያ ደረጃ ወደ አገር ቤት የሚገቡ የማያስፈልጉ የቅንጦት ዕቃዎችን መጠን መቀነስና ቀረጣቸውን መጨመር ያስፈልጋል። በተጨማሪም ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ መጠጦችና የምግብ ዐይነቶችን መከልከል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የከረንሲ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። የውጭ ምንዛሪ የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ለማስመጣት የሚታደል መሆን አለበት። በሶስተኛ ደረጃ፣ አገሪቱ ቀሰ በቀስ ከቡናና ይህን ከመሳሰሉት የጥሬ ሀብቶች በመላቀቅ የኢንዱስትሪ ምርቶችን እያመረተች የምትልክበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በዚህ መልክና በተለያዩ ወደ ውስጥ ባተኮረ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ፖሊሲ(Inward-Looking Strategy)አማካይነት ኢኮኖሚዋን በማሳደግ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ መመካቷን ልታቆም ትችላለች።

7ኛ) ከዚህ ስንነሳ ሁለንታዊ(Holistic Model) የሆነ የኢኮኖሚ ዕቅድ ማውጣት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ አገዛዙ እስከዛሬ ድረስ ከሚገለገልበት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅ ያስፈልጋል። ከዚህም ባሻገር ከውጭ የሚመጣን ተፅዕኖ መቋቋም በጣም አስፈላጊና ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ነው። እስካሁን ድረስ ወያኔ የተከተለው የኢንዱስትሪ ተከላ ፖሊሲ ሀብትን ሊፈጥርና ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲስፋፉ የሚያመች አይደለም። የቢራ ተከላና ሌሎች የመጠጥና የምግብ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት በመሰረቱ ዕውነተኛ የስራ-ክፍፍልንና ሀብትን ሊፈጥር አይችልም። የድሮው ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀም በመስፋፋት ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ እንጂ አምራችና ፈጣሪ ሊሆን አልቻለም። ብዙዎቹን ኢንዱስትሪዎችንም ስንመለከት በጥሬ-ሀብትና በመለዋወጫ ዕቃዎች ከውጭ በሚመጡ ጥገኛዎች ናቸው። ለምሳሌ የቢራ ፋብሪካ ተቋቁሞ ድፍድፉ ከውጭ ነው የሚመጣው። አገሪቱ ውሃ ብቻ ነው የምታቀርበው ማለት ነው። ስለዚህም ከዚህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ተከላ ዘዴ መላቀቅና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት በሚያገለግሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማትኮር እጅግ አስፈላጊ ነው። እርስ በራሳቸው የተያያዙና አንደኛው በሌላኛው ላይ ጥገኝነት ያለው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ(Value Added Chain) ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ህብት ሊፈጠርና የስራ መስክ ተከፍቶ ተጨባጭ ደሞዝ(Real Income or Wage) ሊያድግ የሚችለው።

ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል ከተማዎች ከታች ጀምረው በዕቅድ መገንባት አለባቸው። ከተማዎችና መንደሮች ሲገነቡ ብቻ ነው ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማስፋፋት የሚቻለው። አብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የማይሆን የኢንዱስትሪ ተከላ ስልት በመከተል ሊወጡት የማይችሉት ችግር ውስጥ ገብተው እናያለን። መቅደም ያለባቸውን ነግሮች ትተው ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማትኮር ያልተስተካከለ ዕድገት በመፍጠር በየከተማዎች ውስጥ  የህዝብ መጨናነቅ እየተፈጠረ ነው። የብራዚል ትላልቅ ከተማዎች ችግር ከተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊስና የኢንዱስትሪ ተከላ ጋር የተያያዘ ነው። ከተማዎች የሴተኛ አዳሪዎችና የማጅራት መቺዎች መፈልፈያዎች በመሆን በመንግስትና በህዝብ       መሀከል ፍጥጫ የተፈጠረበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ከተማዎችና መንደሮች ጥበባዊ በሆነ መንገድ ሲገነቡ ብቻ ነው የኋላ ኋላ የዕደ-ጥበብ ሙያና ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በማደግ ለኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት መጣል የቻሉት። ይህ ነው ክላሲካልና ትክክለኛው የዕድገት ጉዞ።

ስለሆነም ከከተማዎችና ከመንደሮች ግንባታ ጋር የሚሂዱ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። ይህንን በሚመለከት የየክልሉ አስተዳዳሪዎች የኢንዱስትሪ ተከላ ፖሊሲ በማውጣት ለኢንቬስተሮች አመቺ ሁኔታን መፍጠር አለባቸው። ለምሳሌ በክሬዲትና በቀረጥ ፖሊሲ አማካይነት ኢንቬስተሮችን መማረክ   ይችላሉ። በዚህ ረገድ ከዚህ ጋር ተያይዘው ሊሄዱ የሚችሉ የገበያ አዳራሾችንና የመገበያያ ቦታዎችን በዕቅድና ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባትና ማስፋፋት እጅግ አስፈላጊ ነው።

8ኛ) ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎን ለማስፋፋት የግዴታ እንደተግባረ-ዕድ የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ማስተማሪያና ማሰልጠኛ መስኮችን በየቦታው ማስፋፋት ያስፈልጋል። በዚህ መስክ ጠለቅና ስፋ ያለ ልምድ ካላቸው እንደአውስትሪያና ጀርመን ከመሳሰሉት አገሮች ጋር ልዩ ስምምነት ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ከእነዚህ አገሮች በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ያተኮረ የመዋዕለ-ነዋይ ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል። የምንፈልገው ቲክኖሎጂን በመኮረጅ ለማዳበርና ለማስፋፋት ስለሆነ በተለይም ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚተከሉቡትን፣ እዚያው ምርምርና ጥናት እየተካሄደ የሚዳብሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።

9ኛ) ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት በመንግስት የሚደገፍና የሚደጎም የሳይንስ ምርምር ጣቢያዎች በየቦታው ማቋቋም። ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በቀጥታ የምርምርና የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች  እንዲሆኑ መንግስትና የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ምሁራን ርብርቦሽ ማድረግ አለባቸው።

10ኛ) ይህንን ሁሉ ፋይናንስ ለማድረግ ራሱን የቻለ ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲይስተም ማቋቋም ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ የክሬዲት ባንክ ራሱ ልዩ ሰርቲፊኬቶችን ወይም ቦንዶችን በማተም በህዝብ ውስጥ ያለን ገንዘብ በወለድ በመሳብ፣ ይህንን ገንዘብ እንደገና ለኢንቬስተሮች በማበደር ዕድገትን ማፋጠን ይቻላል። አብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታት የሚሰሩት ስህተት ካለዶላርና ኦይሮ አንድን አገር መገንባት የሚቻል ስለማይመስላቸው የባሰ የዕዳ ውጥመድ ውስጥ በመግባት አገሮቻቸውን እያፈራረሱ ነው። የማያስፈልግ የሞኔተሪ ወይም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ሀብት ያወድማሉ። የባሰውኑ ጥገኛ እንዲሆኑ ይገደዳሉ። ስለሆነም ለአንድ አገር ዕድገት ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል ከውጭ የሚመጣ ብድር ሳይሆን ከውስጥ በልዩ ቲክኒኪ የሚዘጋጅ የብድር አሰጣጥ ሲይስተም ነው። የአንድ አገር ገንዝብ ከምርት ክንውን ጋር በጥብቅ ከተያያዘና ቶሎ ቶሎ የሚሽከረከር ከሆነ የመግዛት ኃይሉም ይጠነክራል።

11ኛ) አጠቃላይ ዕድገትን ለማፋጠን የግዴታ ምግብ ለስራ(Food for Work Program) የሚባል የሃያና የሰላሳ ዐመት ዕቅድ ማውጣት አስፈላጊ ነው። ይህንን በስራ ላይ ለማዋል በተለይም ውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በየወሩ አንድ መቶ ዶላር ቢያወጣ ይህንን ገንዘብ በመሰብሰብና ተግባራዊ በማድረግ ከተማዎችን፣ የባህል ማዕከሎችን፣ የገበያ አዳራሾችን፣ መንገዶችን፣ ቤቶችንና ድልድዮችን በመስራት አገርን መገንባት ይቻላል። በዚያው መጠንም ለሚሊዮን ህዝብ የስራ መስክ መክፈት ይቻላል። የሚከፈለው ደሞዝ በዐይነትና በገንዘብ ሲሆን አዲስ የስራ ባህል እንዲፈጠር ያግዛል።  ስለሆነም የተወሰነው ገንዘብ ባንክ ውስጥ በመቀመጥና የወለድ ወለድ በማግኘት ገንዘቡ ራሱ በራሱ ሊባዛ ይችላል። ያም ሆነ ይህ ይህ ዐይነቱ ፕሮግራም ቢያንስ ከሃያ እስከ ስላሳ ዐመት ያህል የሚፈጅና በልዩ ኢንስቲቱሽን የሚመራ መሆን አለበት።

12ኛ) እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግ የግዴታ ወያኔ የዘረጋውን የጭቆና መዋቅርና የስለላ ድርጅት ማፍረስ ያስፈልጋል። ወያኔ እንደፖለቲካዊ ኃይል እስካለና በፖለቲካ ሂደት ውስጥ እስከተሳተፈ ድረስም በአገራችን ምድር መሰረታዊ ለውጥ በፍጹም ማምጣት አይቻልም። ህዝባችን እስከዛሬ ድረስ በወያኔና በግብረአበሮቹ ከፍተኛ ግፍ ተፈጽመውበታል። ወያኔም ራሱን ለማሻሻልና ህዝባዊ ባህርይ ሊኖረው እንደማይችል በ27 ዓመታት የአገዛዝ ታሪኩ ውስጥ አረጋግጥጧል። ስለሆነም ወይኔ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ እስከቀረ ድረስ በአገራችን ምድር ሰላምና መረጋጋት በፍጹም ሊመጡ አይችሉም። ሰላምና መረጋጋት በሌሉበትና ህዝቡም እርግጠኝነት በማይሰማው አገር ውስጥ ስለመሰረታዊ ለውጥ ማውራት በፍጹም አይቻልም። የኛም ተግባር ያለውን ፖለቲካዊ ሂደት በማፋጠን ወያኔ ከህዝቡ የሚነጠልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ወያኔ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ እስከቀረ ድረስ የውጭ ኃይሎች እሱን መሳሪያ በማድረግ ህዝባዊ መተላለቅ እንዲመጣ ስለሚያደርጉ የዚህ ኃይል መበታተን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ስለሆነም ከውጭ ኃይሎች ጋር በተለይም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ያለንን ግኑኝነት መታየትና መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው።

በአጭሩ አንድን ደካማ አገር ለመገንባት የግዴታ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል። አንድ አገር ሊያድግ የሚችለው ከውጭ በሚመጣ ዕርዳታ ሳይሆን በራሱ ጥረት ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የሃሳብ ጥራትና ቆራጥነት፣ እንዲሁም አገር ወዳድነት ያስፈልጋል። የማያስፈልግ የፖለቲካ ሽኩቻና የቡድን ፖለቲካ አንድን አገር ያዳክማል። ለስልጣኔና ለዕድገት እንቅፋት ይሆናል። ስለሆነም ኢትዮጵያን ማዳከምና መበታተን፣ እንዲሁም ማሳደግና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ማድረግ በእጃችን ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው። ለጥፋቱም ሆነ ለልማቱ ተጠያቂዎቹ እኛው ብቻ ነን። መልካም ግንዛቤ !!          

fekadubekele@gmx.de