[gtranslate]

የማህበራዊና የህብረተሰብአዊ ጥያቄ ወይም የብሄር/ብሄረሰብ ጥያቄ ?

                   እባብ ወተት ጠጥታ  መርዝ ትተፋለች፣ ቅዱስ ግን መርዝ ጠጥቶ ወተት ይተፋል !“ Azmuto

                                                                                     ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

መጋቢት 25፣ 2019

መግቢያ !

አሁን ያለንበት ዘመን 21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው።  ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ ብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና አሜሪካንንም ጨምሮ፣ እንዲሁም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ ዛሬ ደግሞ ቻይና በሳይንስ አማካይነት የቴክኖሎጂን ምጥቀት በማግኘት አነሰም በዛም የተረጋጋ ህብረተሰብ ለመገንባት ችለዋል።  በተለይም ባለፉት 40 ዓመታት የተፈጠሩትና ገበያ ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎች ቀደም ብለው ከነበሩት ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲወዳደሩ በጥራትም ሆነ በምቾት እጀግ ተሽለው የሚገኙ ናቸው። የዛሬ አርባ ዓመት ገበያ ላይ የነበሩና ለፍጆታ የቀረቡ ምርቶች ዛሬ በፍጹም አይታዩም። እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች እጅግ ከመሻሻላቸው የተነሳ በተወሰነ ሰዓትና የሰው ኃይል ብዙ ምርቶችን ማምረት የሚቻልበት ወቅት ውስጥ ነው የምንገኘው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣  መኪናንና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በግማሽ ወይም በሙሉ አውቶማቲክ ወይም ሮቦታ እየታገዙ ነው የተለያዩ ክፍሎችን የሚገጣጥሙትና ወደ አንድ ወጥ ምርትነት የሚለውጡት።

ሰልሆነም በዚህ የቴክኖሎጂ ዓለም በመታገዝ እኛም በብዙ ሺህ ማይልስ የሚቆጠር ርቀትን አልፈን  መጥተን አውሮፓና አሜሪካ፣ እንዲሁም ሌላ ሰለጠነ የሚባለው ዓለም ውስጥ ተበታትነንና ተደላድለን በመኖር የቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚዎች ለመሆን በቅተናል። አዳዲስ መኪናዎችን የምናሽከረክር፣ በኢንተርኔት ዓለም ውስጥ በመኖር ኢንፎርሜሽኖችን አንድ ደቂቃ በማይፈጅ ጊዜ ውስጥ የመለዋወጥ እድል አለን። የምንኖርበት ቤትም ማንኛውንም ነገር ያሟላ ነው። እነዚህ ሁሉ ቴክኖሎጂዎች የተገኙት ዝም ተብለው አይደለም፤ ወይም ከሰማይ ዱብ ብለው የወረዱ አይደሉም። ከፍተኛ ምርምርንና ሙከራን በማድረግ ነው ቴክኖሎጂዎቹ የተገኙት። የጥቂት አገሮችና ህዝቦች የስራ ውጤቶች በመሆን ከእነሱ አልፈው የዓለም ማህበረሰብ እንዲጠቀምበት አድርገዋል። እስቲ እናስብ የአውሮፓ አገሮችና ሌሎችም የሃይ-ቴክ ባለቤት የሆኑ አገሮች እድሜያቸውን በሙሉ የሚሆን የማይሆን ነገር አንስተው ቢጨቃጨቁ ኖሮ እንደዚህ ዓይነቱን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ማየት ይችሉ ነበር ወይ? በፍጹም ! አንድም እርምጃ ወደ ፊት መራመድ ባልቻሉም ነበር። የእነሱ እጣ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው የዓለም ህዝብም እጣ የጨለማና የድህነት ኑሮ በሆነ ነበር። እንደኛው በድህነትና በረሃብ እንዲሁም በስደት በማቀቁ ነበር።

ወደ እኛ አገር ስንመጣ፣ ምናልባት ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት የተነሳ የብሄረሰብ ችግርና ጭቆና የሚሉት ነገር ጭንቅላታችንን ወጥሮት ዛሬም እንደ አዲስ አጀንዳ ይዘን ስንጨቃጨቅ እንገኛለን። ዋናው ችግራችንና የስልጣኔውም ቁልፍ እሱን በመፍታት ብቻ ይገኝ ይመስል፣ ብሄሬ ተበደለ፣ ተጨቆነ፣ ተናቀ፣ አማርኛን ተገድጄ ነው የተማርኩት፣ መለያዬን እንደገና መልሼ ማግኘት አለብኝ በማለት ያልተወራረደ ሂሳብ ያለን ይመስል በዚህና ሌሎች እልክ አስጨራሽና፣ የሰውን ጭንቅላት ወጥረው በሚይዙ፣ ግን ደግሞ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ለመፍታት በማይችሉ ነገሮች ላይ ስንጨቃጨቅና ሰሚናርም ስናዘጋጅ እንታያለን። ይህንን ያረጀና በታሪክ ውስጥ ካለማወቅ የተነሳ የተደረጉ ስህተቶችን እየደጋገምን በማንሳት የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት በርዘናል። ለማቲማቲክስ፣ ለፊዚክስ፣ ለኬሚስትሪ፣ ለባዮሎጂና፣ እንዲሁም ለሌሎች የህዝባችንና የአገራችንን ችግሮች መፍቻ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከመረባረብ ይልቅ  የብሄር ጥያቄ የሚሉትን የቅኝ ገዢዎችን የመከፋፈያ አስተሳሰብ የራሳችን በማድረግ ሃምሳ ዓመት ያህል እርስ በእርሳችን ተከሳክሰናል። ጦርነት ከፍተን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲያልቁ አድርገናል። ከፍተኛ የታሪክና የባህል ወንጀል ሰርተናል።

የዛሬው የአገራችንን ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፣ ህዝባችንም የመረረ ትግል በሚያደርግበት ወቅት አንዳንዶች የትግሉን አቅጣጫ ለማዘናጋት የብሄረሰብን አጀንዳ እንደዋና የችግሩ ምንጭ አድርገው በማንሳት ወጣቱን በስሜት እየቀሰቀሱትና የማሰብ ኃይሉን ችግርን በማይፈታ ነገር ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ላይ ናቸው። እንደሚታወቀው፣  በተለይም ኋላ-ቀሩ በሚባሉ አገሮች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችና በህዝብ ላይ በተለያየ መልክ የሚደርሱ ጭቆናዎች አብዛኛውን ጊዜ ካለማወቅ የተነሳ ነው። ህብረተሰብአዊ ተሃድሶ በሌለበትና ብዙ ነገሮች በዘልማድ በሚሰሩበት አገሮች ውስጥ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የአንድ ህዝብ ኑሮ መሻሻልና ነፃ መውጣት ጉዳይ እስከዚህም ድረስ የሚታያቸው አይደለም። እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ የነበረው የአገራችን አስተሳሰብ ይህንን ይመስል ነበር ብሎ ከሞላ ጎደል መናገር ይቻላል። ከዚህ ስነነሳ ቀደም ብለው የተነሱት የመደብና የብሄረሰብ ጥያቄዎች የአገራችንን መሰረታዊ ችግሮች ያላገናዘቡ፣ የሳይንሰን መሰረተ-ሃሳብ ያልተከተሉ፣ በተለይም በጭንቅላት ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችን ያላወጡና ያላወረዱ ነበሩ። በመሆኑም ዛሬም እንደትላንትናው ከዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ባለመላቀቅ ያለንበትን ሁኔታ በመረዳትና ትግላችንን በሃሳብ ዙሪያ አሰባስበን ከመታገል ይልቅ ጊዜው እንዳያመልጠን በማለት ኃይልን በሚበታትንና የአገራችንንም ችግር በማይፈታ ላይ እንረባረባለን። የ27 ዓመቱ የአንድ ብሄር ኃያልነት የሰፈነበት የጭፍጨፋና የዘረፋ ዘመን አለፈ ስንልና ደስታችንን ሳናጣጥመው፣ ጊዜው የኛ ነው ብለው በተነሱ፣ የታሪክን ኃላፊነት ባልተገነዘቡና ሞራላዊ ግዴታ በማይሰማቸው ኃይሎች አገራችንና ህዝባችን ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንዲያመሩ እየተደረገ ነው። መሰረታዊ በሆኑ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ፣ ማለትም ድህነትን መቅረፍ፣ የስራ መስክን መክፈትና ለወጣቱም የሙያ ስልጠና ከማቋቋምና አገራችንን በፀና መሰረት ላይ ከመገንባት ይልቅ አሁንም እንደትላንትናው  የተያዘው ፈሊጥ በዚህም በዚያም ብሎ የአንድ ብሄረሰብ የበላይነት ማስፈን ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ያለውን ችግር የሚፈታ ሳይሆን የሚያባብሰውና ለአዲስ የወንድማማቾች ጦርነት የሚጋብዘን ነው። ፖለቲካ ሳይሆን ተራ ሽወዳና አገራችን በውጭ ኃይሎች እንድትወረር  የሚያድረግ አደገኛ አካሄድ ነው።

ይህንን መሰረት በማድረግ በምንም ዐይነት የአንድን ህብረተሰብ መፍታት የማይችለውን የብሄረሰብ ጥያቄ እየተባለ የሚወተወተውን ኢ-ሳይንሳዊ ጽንሰ-ሃሳብ ለማሳየት እሞክራለሁ። ከዚህም በመነሳት የአንድ ህዝብ መሰረታዊ ችግሮችና አትኩሮዎች የማህበረሰባዊ ችግሮች(The Social Question) መሆናቸውን ለማረጋገጥ እሞክራለሁ።

ለመሆኑ ብሄር የሚባል ነገር አለ ወይ ?

በመጀመሪያ አንድ ሰው ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ ከሚባለው ክፍል መወለዱ ተፈልጎና ተመርጦ አይደለም። አንድ ሰው እንደ ሰው ሆኖ ነው እንጂ የሚወለደው እንደ ብሄረሰብ ሆኖ አይደለም የሚወለደው። ስለሆነም የአንድ ሰው መለኪያው ልክ እንደማንኛውም ሌላ ሰው፣ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጡ አካልና ልዩ ልዩ ባህርዮችን ያዘለው አዕምሮ ሲኖሩት ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ የሰው ልጅ ውስጠ-ኃይል ስላለው አንድ ቦታ ረግቶ ስለማይኖር ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመጋባት ልጆች ይወልዳል። በዚህም የተነሳ በተለያዩ ብሄረሰብ እየተባሉ በሚጠሩ የሰው ልጆች  ዘንድ በመጋባት የተነሳ አንድ ወጥ ባህል ሳይሆን ከተለያዩ ብሄረሰቦች ተጨምቆ የሚወጣ ባህል የሚሉት ነገርና በአንድ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የሚያግባባ ቋንቁ ይፈጠራል። በሌላ አነገጋር፣ በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ ብሄረሰብ እየተባሉ የሚጠሩ ሰዎች ቢኖሩም ይህም ማለት በንጹህ መልክ አንተ ኦሮሞ ነህ፣ አንተኛው ደግሞ አማራ ነህ፣ አንቺ ኩሎ ኮንታ ነሽ እያሉ መናገር በፍጹም አይቻልም። አንድ ሰው የአንድን ብሄረሰብ ቋንቋ አቀላጥፎ በመናገሩ ብቻ አማራ ነው ወይም ኦሮሞ ነው የሚያስብለው አንዳች ነገር ሊኖር አይችልም። ስለሆነም አንደኛው  አንድ አካባቢ በመወለዱና በማደጉ ብቻ አማራ፣ ጉራጌ ወይም የም ወይም ሌላ እየተባለ እየተፈረጀበት፣ ከሌላው እሱን መሰል ከሆነው በእግዚአብሄር አምሳል ሆኖ ከተፈጠረው ወንድሙ ወይም እህቱ ጋር የሚያጣላው ምንም ምክንያት የለም።

ወደ ታሪካዊ ሁኔታዎች ስንመጣና የአገራችንን ሁኔታ ስንመረምር፣ በተለይም ከአንደኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ የገዢ መደቦች፣ ለመስፋፋት ሲሉ በሃይማኖትና እንዲያም ሲል በጦርነት አንዳንድ ግዛቶችን በመያዝና በቁጥጥራቸው ስር ካደረጓቸው የገዢ መደቦች ጋር በመጋባት ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ እምርታን ሊሰጡ ችለዋል። ስለሆነም አማራዎችን ይወክላል የሚባለው የገዢ መደብ በ14ኛው ክፍለ-ዘመን በመጀመሪያ ግዛቱን ለማስፋፋት ሲል አስተማሪዎች በደቡቡ ክፍል በማሰማራት የክርስትናን ሃይማኖት በማስተማርና እዚያ ካሉት ብሄረሰብ ተብለው ከሚጠሩት ጋር በመጋባት በአካባቢው ልዩ ዐይነት ባህል ሊስፋፋና ሊዳብር ችሏል። በመሆኑም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛትና የደቡቡን ክፍል በሚገዙት አምስት ንጉሳዊ አገዛዞች መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። ይህ እንግዲህ ኦሮሞዎች ዛሬ ኦሮሚያ እያሉ የሚጠሩትን ግዛት ከመውረራቸው በፊት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ኦሮሞዎች ከአንድ አካባቢ በመነሳትና ቀስ በቀስ አምስቱን የደቡቡን ንጉሳዊ አገዛዞች በመደምሰስ የራሳቸውን ግዛቶች ይመሰርታሉ። ቀድሞ የነበሩ የከተማና የመንደሮችን ስሞች በመቀየር ሌላ የኦሮምኛ መጠሪያ ስም ይሰጧቸዋል።  ቀስ በቀስም  ከከብት አርቢነት ወደ ተቀማጭ አራሽነትና መሬትንም በመቆጣጠር የገዢ መደብ ባህርይን ያዳብራሉ። ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሲያመሩ ደግሞ በዚያ አካባቢ ብዙ ጉዳት ካደረሱና ብዙ ህዝብ ከጨረሱ በኋላ ቀሰ በቀስ ከተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመጋባት እዚያ ለነበረው ባህል ልዩ እምርታን ይሰጡታል። ወደ ገዢ መደብነትም በመቀየር ታሪክን ሰሪ ለመሆን ችለዋል። በሌላ አነጋገር፣ ልክ እንደ ሌሎች አገሮች መዋጥና መዋዋጥ እንዳለ ሁሉና፣ አንደኛው ሌላውን አሸንፎ አንድ ትልቅ አገር ለመግዛት እንደሚፈልግ ሁሉ ይህም ዐይነቱ ታሪካዊ ግዴታና ድርጊት በኛ አገርም ተካሂዷል። የሚያሳዝነው ግን ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጡ ቡድኖችም ሆነ ግለሰቦች የራሳቸው ብሄረሰብ ሲስፋፋ ያደረሰውን በደልና ዝርፊያ ወደ ጎን በመተው እነሱ ብቻ ተጎጂዎች የሆኑ በማስመሰልና በማውራት ታሪክን በማጣመምና የማይሆን ነገር በማውራት ሰውን ለማሳመን ሲሞክሩ ስናይ እነዚህ ሰዎች የቱን ያህል የታሪክ ሂደትና የህብረተሰብ ዕድገት ያልገባቸው መሆኑን እንመለከታለን።

ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአገራችን ምድር አዲስ የተፈጠረው ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት ከካፒታሊዚም ጋር በጥብቅ የሚገናኝና የሚተሳሰር ነው። ውስን በሆነ መልክ የገባው ካፒታሊዝም የተወሰነ የህብረተሰብ ግኑኝነት እንዲፈጠር ቢያደርግም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባልተስተካከለ ዕድገት ምክንያት የተነሳ በአንድ አካባቢ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን ከ90% በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል በድህነትና ኋላ-ቀር በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚኖር ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ያልተስተካከለ ዕድገት ከተሳሰተ የዘመናዊነት(modernization) አገባብና ሂደት ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀርቶ የብሄረሰብ ጭቆናና የመደብ ችግር ተብሎ በመወሰዱ እንደዚህ  ዐይነት የተሳሰተ ምሁራዊ ግንዛቤ  አሉታዊ ኃይል(Negative Energy) ያላቸው  ኃይሎች ብቅ እንዲሉና አለመረጋጋት እንዲኖርና፣ በተለይም በተወሰኑ አካባቢዎች ጦርነት እንዲስፋፋ በማድረግ የአገሪቱን አንድነትና ቀስ ብሎ በጥገናዊ መልክ የማደግ ዕድል መፈታተን ጀመሩ። ረጋ ካለና ጥልቅነት ካለው ምሁራዊ ጥናትና ውይይት ይልቅ በተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ በማትኮር ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ አጀንዳዎች ትኩረት እንዳይሰጣቸው አደረጉ። የኢትዮጵያ ዋናው ችግር አገሪቱ የብሄረሰቦች እስር ቤት በመሆኗ ነው የሚለውን ኢ-ሳይንሳዊና ምሁራዊነት የሌለውን የተረት ተረት በማስፋፋት አንድ ህዝብ ታሪክን እንዳይሰራ አገዱት። በተለይም ወያኔ ስልጣንን በበላይነት በሚቆጣጠርበት ዘመን ለብዙ ዘመናት ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ይጠቀምበት የነበረው ፖሊሲ የብሄረሰብን ጥያቄ  ዋናው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ መሳሪያ በማድረግ ነበር። ከሞላ ጎደል ወያኔ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ደግሞ የህዝባችንን ዕውነተኛ የነፃነትና የስልጣኔ ጥም የተገነዘቡ ኃይሎች ፍላጎቱን ለማዳፈንና የጨለማውን ዘመን ለማርዘም  ማንም ሳይመርጣቸው የኦሮሞ ብሄረሰብ ተጠሪ ነን በማለት ፖለቲካውን በመጥለፍና (Highjack) ለራሳቸው የአጭር ጊዜ መጠቀሚያ በማድረግ በወንድማማች ህዝብ መሀከል መተማመን እንዳይኖርና የመጨረሻ መጨረሻ በውጭ ኃይል የሚደገፍ ፈሺሽታዊ አገዛዝ ለማስፈን ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ። ወጣቱን ያሳስታሉ። እንደፈለጋቸውም በመውጣትና በመግባት ቅስቀሳ በማድረግ የፖለቲካውን አየር ሊበርዙት ችለዋል። እንዲከፍቱ በተፈቀደላቸው የዜና ማሰራጫ አማካይነት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ዜና አይሉት ነገር በማናፈስ ህዝባዊ ዕልቂት እንዲፈጠር በማድረግ ላይ ናቸው። ለዚህ ድርጊታቸው ደግሞ የኢትዮጵያዊነትን አርማ የለበሱ የዜና ማሰራጫዎች እየተባበሯቸው ነው። በዚህ አካሄዳቸው ግን እንታገልለታለን የሚሉትን ብሄረሰባቸውንም በፍጹም አይጠቅሙትም። የድህነቱንና የኋላ-ቀርነቱን ዘመን ከማራዘም በስተቀር ምንም ፋይዳ ሊሰሩ አይችሉም። የሚፈልጉትንም ነፃነት ሊቀዳጁም በፍጹም አይችሉም።

            የአገራችን ችግር ማህበራዊና ኋላ-ቀርነት እንጂ የብሄረሰብ ጥያቄ አይደለም!  

የአለፉትን 60 ዓመታት የአገራችንን የመንግስት አወቃቀርና ከዚህ የሚመነጨውን ፖሊሲ ለተከታተለ፣ ሶስቱም አገዛዞች በሳይንስ የተጠና፣ ፊሎሶፊንና ቲዎሪን መሰረት ያደረገ፣ አገራችንን ዘመናዊና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊያደርጋት የሚችል ፖሊሲ እንዳልነበራቸው መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም አንድ ህዝብ ኋላ-ቀር ከሆነ አኗኗር ስልት ተላቆ ምርታማነትን በማሳደግ ኑሮውን በማሻሻል ሰፋ ያለና ጠንከር ያለ ህብረተሰብ እንዲመሰርትና ተከታታይነት እንዲኖረው የወሰዱት ሳይንሳዊ ፖሊሲ በፍጹም አልነበረም። በመሆኑም የአገራችንን ሁኔታና የህዝባችንን ፍላጎት ያላገናዘበና፣ የተከታታዩንም ትውልድ እጣ ቁጥር ውስጥ ያላስገባ በውጭ ኃይሎች የተነደፈ ወይንም ሳያወጡ ሳያወርዱ ተግባራዊ ያደረጉት ፖሊሲ በአገራችን ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር አድርጓል።  አንድ አገር ያላትን ተፈጥሮአዊ ሀብት በስነስርዓት መጠቀም የማይችልና ድህነትን ለመቅረፍ ቀን ከሌሊት ደፋ የማይል አገዛዝ በመሰረቱ ጥሎ የሚያልፈው ያልተረጋጋና በሆነው ባልሆነው የሚናቆር ህዝብ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ በሰፊ የኢኮኖሚና የማህበረሰብአዊ መሰረት ላይ ያልተገነባ አገር ደግሞ መጥፎ ህልም ለሚያልሙ ትንሽ ተማርን ለሚሉ የውስጥ ኃይሎችና፣ የአገራችንን መዳከምና እንዲያም ሲል መበታተን ለሚፈልጉ ኃይሎች ቀዳዳ መስጠቱ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ስለሆነም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የብሄረሰብን ጥያቄ አንግቦ ነፃ እወጣለሁ ያለ ኢትዮጵያዊ ኃይል በሙሉ በህዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት ያወጀው በውጭ የስለላ ኃይሎችና በአካባቢው የሚገኙ የአገራችንን መጠናከርና መረጋጋት በማይፈልጉ አጎራባች አገሮች በመታገዝ ነው። እነዚህ የውስጥ የነፃነት አራማጅ ኃይሎች ነን የሚሉ በራሳቸው ላይ አጉል ዝቅተኛ ስሜት በማሳደርና ወጣቱን በመቀስቀስና አመፀኛ እንዲሆን በማድረግ እንዳየነውና እንደቀመስነው ለብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው ህይወት መጥፋትና፣ አገራችንም አሁን ባለችበት ሁኔታ እንድትገኝ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። በቡሃ ላይ  ጆሮ ደግፍ ተጨምሮበት እንደሚሉት አነጋገር፣  ሌሎችም ከብሄረሰብ ጋር ያልተያያዙ ኃይሎች የውጭ የስለላ ኃይሎች የሚሰጧቸውን ምክርና የገንዘብ ድጋፍ ተገን በማድረግ አገራችንን ከውስጥ ሆነው በፊዩዳላዊ ተንኮል ቦርብረው አዳክመዋታል። እነዚህ ኃይሎች በተለይም  ቀደም  ብለው ከነበሩት የገዢው መደቦች ጋር በጥብቅ የተሳሰሩና ዝምድናም የነበራቸው ሲሆኑ፣ ዋናው ዓላማቸው በተለይም ኢትዮጵያ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ጠንካራ አገርና ህብረተሰብ እንዳትመሰርት ማድረግ ነው። በዚህ ዐይነቱ እርኩስ ተግባርም የማርክሲዝምን አርማ አንግቦ እታገላለሁ ይል የነበረው ኃይል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአገራችንን ውድቀት አፋጥኗል ማለት ይቻላል።

ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ፣ በተለይም እንደነ ጃዋር የመሳሰሉት አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናይ ነን ብለው የፖለቲካን ትርጉም ሳይረዱ የተሰጣቸውን የሚዲያ ዕድል በመጠቀም የሚያስፋፉት ቅጥ ያጣና የተዘበራረቀ ልፍለፋ የፖለቲካውን  ትግል እያዘበራረቀውና አብዛኛውንም ህዝብ ግራ እያጋባው እንደመጣ እንመለከታለን። ጃዋርና ተከታዮችም ሆነ በዳውድ የሚመራው የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት የብሄረሰብን ጥያቄና ነፃነት ማግኘት አለብን የሚለውን ከማራገብና ህዝብን ከማወናበድ በስተቀር፣ ይህ ነው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲያችን ብለው ሲያስተምሩና ሲከራከሩ በፍጹም አይታዩም። በመሰረቱ ሳይንስን፣ ፍልስፍናንና ቲዎሪን መሰረት አድርጎ የማይካሄድ ትግል ወደ ፋሺዝም ነው የሚያመራን። እንደሚባለው፣ እንዳየነውና በታሪክም እንደተረጋገጠው በብሄረሰብ ላይ የተመረኮዘ ናሺናሊዝም የመጨረሻ መጨረሻ  ዘረኛና ሌላውን በመጥላት ቀስ በቀስ ደግሞ ወደ ፋሺዝም የሚያመራ አካሄድ ነው። ሂትለር ለጀርመን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉትን አይሁዲዎችን በመጥላትና ዝቅተኛ ስሜትም ስላደረበት  ነው ዘመቻ ያደረገባቸውና የመጨረሻ መጨረሻም ለስድስት ሚሊዮን ሰዎች ማለቅ ምክንያት የሆነውና ሆሎኮስት የሚባለውን ዘግናኝ ድርጊት የፈጸመው። እነ ሻቢያና ህውሃት የሚባሉትም  ገዢዎች በአጀማመራቸው የማርክሲዝምን አርማ ይዘው ቢነሱም ዋናው ዓላማቸው የአማራውን ህዝብ ቅስም ለመስበርና እነሱ በጭንቅላታቸው ውስጥ የቀረጹትን የአማራውንንና የኦርቶዶክስን ሃይማኖት የበላይነት ማዳከምና የራሳቸው የበላይነት  ለማረጋገጥ ነው። ድርጊታቸው ከፋሺዝም የሚያንስ አይደለም ማለት ነው።

በአገራችን ምድር እስካሁን ድረስ የተካሄዱት ትግሎች በሙሉ ራሳችንን የሚያዳክሙ እንጂ ለማንም የሚጠቅሙ አይደሉም። የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን ዕድገት፣ ከዚህም በላይ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ያለን ምሁራዊ ድክመትና፣ ጠለቅና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖር ያላገናዘቡ በመሆናቸው እርስ በእርሳችን እንድንፋተግ ተደርገናል። የድንቁርናችን ሰለባ በመሆን ተባብረንና ተቻችለ ታሪክን ከመስራት ይልቅ የውጭ ኃይሎች ተጠሪና ተመካሪ በመሆን የአገራችንን ውድቀትና መበታተን እያፋጠን እንገኛለን። የተማርነው ትምህርት ሁሉ ጭንቅላታችንን አንጾት የተቀደሰ ተግባር ከመስራት ይልቅ መጥፎ ነገር እንደተማርን ይመስል በክፉኛ መቀናናትና መጠላላት በመወጠር መስራት ያለብንን ነገር እንዳንሰራ ታግደናል። ይህ ዐይነቱ ታሪክን ያላገናዘበ ትግል ግን አንድ ቦታ ላይ መገታት አለበት። እያንዳንዱ ምሁር ራሱን በራሱ በማግኘት ታሪክ ሰሪነቱንም የሚያረጋግጥ መሆን አለበት እንጂ የአገራችንን ውድቀት ለማፋጠን ከውጭ  ኃይሎች ጋር መስራት የለብትም። እርስ በእርስ መመካከርና ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥ እንጂ ከውጭ ኃይሎች ምንም ዐይነት ምክር የሚጠይቅበት ምክንያት የለውም።

የኦሮሚያን ሪፐብሊክ እንመሰርታለን ብለው ደፋ ቀና ለሚሉት ኃይሎች የመጨረሻ ጥሪዬ፣ በኢትዮጵያ ምድር ታሪክን ልትሰሩ የምትችሉት በዚህ ዐይነቱ አካሄድ ሳይሆን፣ ከሌላው ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር በመመካከርና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ብቻ ነው። ዓላማችንም ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚስማምና ተደላድሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚያስችለውን አገር መገንባት ብቻ ነው። ስለሆነም የብሄረሰብና የሃይማኖት ጥያቄዎች የህብረተሰብ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉም። የአንድ ህብረተሰብ ችግር በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። የንጹህ ውሃ፣ በቂ ዳይትን የሚሰጥ ምግብ፣ በደንብ የተሰራ መጠለያ፣ ህክምናና ጭንቅላትን ክፍት የሚያደርግና፣ ሰው መሆናችንን እንድንገነዘብ የሚያደርገው ሁለ-ገብ ትምህርት የጠቅላላው ህዝብ ፍላጎትና ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎችና የህዝብ ፍላጎቶች መልስ መስጠት የምንችለው በተናጠል በመታገልና የራሴ አጀንዳ አለኝ በማለት ሳይሆን፣ በአንድ የአስተሳሰብ ዙሪያ ስንሰባሰብ ብቻ ነው። ዛሬ ሰለጠኑ የሚባሉ አገሮች ቀናውን መንገድ በመከተልና በመደማመጥ ብቻ ነው ለማደግና ዓለምን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የቻሉት። ስለዚህም ወዲህና ወዲያ ከመሯሯጣችን በፊት እስቲ አንድ ጊዜ ተቅምጠን የምንሰራውን ስራ ሁሉ እናሰላስል። አስተሳሰባችንን በሙሉ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በፊሎሶፊ ዙሪያ እናድርገው። ለብሄረሰብ ሳይሆን ለነዚህ ነገሮች ቅድሚያ እንስጣቸው።

                                            fekadubekele@gmx.de