[gtranslate]

                                                      

በእግጥስ ኤትኒክ-ፌዴራሊዝም ለአገራችን ጥሩው መፍትሄ ነው ወይ? በርግጥስ ከጎሳ ጋር የተያያዘ የአገዛዝ መዋቅር በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን ተዘርግቶ ነበር ወይ? ከአበበ ገላው ለፕሮፌሰር መሳይ ከበደ  ለቀረበለት ጥያቄ ለሰጠው መልስ የቀረበ ሳይንሳዊ  ትችት !

 

    ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)       

                                ህዳር 12 2023

 

ፕሮፌሰር መሳይ እንደዚህ ብሎ ሲናገር ከምን በመነሳት ነው? እንዴትስ ኤትኒክ ፌዴራሊዝም ጥሩው መፍትሄ ሊሆን ይችላል? የዚህ ወይም የዚያኛው ጎሳ ነኝ የሚለውን ሰፊውን የኦሮሞም ሆነ የሌላ ጎሳ ነኝ የሚለውን ሰፊ ህዝብ መሰረታዊ ችግር ሊፈታ ይችላል ወይ? የአንድንስ ህዝብ ችግር ወደ ብሄረሰብ ወይም ጎሳ መቀነስ ከሳይንስ አንፃር ትክክል ነው ወይ? በመሰረቱ በተለይም በአሁኑ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ጎሳ የሚባል ነገር አለ ወይ? ጎሳ በሚባለው የሳይንስ መሰረት በሌለው ነገር ላይ ስንጨቃጨቅ ሌሎች የአንድ´ን ህዝብና አገር ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮችን፣ ለምሳሌ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ፍልስፍና፣ ሶስዮሎጂ፣ ኢኮኖሚክስ፣ የስነ-ልቦና ሳይንስ፣ በጠቅላላው ጥበብ ብለን የምንጠራቸው ነገሮችን፣ አርክቴክቸርና የከተማ ዕቅድ የመሳሰሉትን. የቴክኖሎጂን ጉዳይ እንዳይዳብሩ መንገዱን አንዘጋም ወይ? ፕሮፊሰር መሳይ ከበደ የፍልስፍና ምሁር እንደመሆኑ መጠን እነዚህንና ሌሎችን ጥያቄዎችን እያነሳ ለመወያየትና ለማስተማር ጥረት ማድረግ  ነበረበት።

በመጀመሪያ ደረጃ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመት ያህል በክልል ደረጃ የተካለሉ ጎሳዎች በአንዳቸውም ቦታ እንደሰው ለመኖር የሚያስፈልጓቸው መሰረታዊ ነገሮች(Basic Needs) ብለን የምንጠራቸው ነገሮች አልተፈቱላቸውም። እደሚታወቀው የሰው ልጅ ለመኖር፣ ለመንቀሳቀስ፣ ለማሰብና ለመስራት የግዴታ የተሟላ ዳዬት፣ ንጹህ ውሃ፣ መጠለያ፣ ህክምና፣ ትምህርትቤትና ሌሎች ነገሮች ያስፈልጉታል። ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ጎሳ የመጣ ሰው ስለጎሳነቱ ከማሰቡ በፊት እነዚህን ነገሮች እንዴት ማግኘት እችላለሁ ብሎ ነው ማሰብ ያለበት። ካለበለዚያ ሊኖር በፍጹም አይችልም። ከዚህ ሃቅ ስንነሳ ወያኔና ግብረ-አበሮቹ አገሪቱን በጎሳ በመከለል፣ በአንድ በኩል የዎር-ሎርድ አስተሳሰብ እንዲዳብር ነው ያደረጉት፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፊው ህዝብ ደንቁሮ እንዲቀር ነው መንገዱን ያመቻቹት። የየክልሉ አስተዳዳሪዎች በአንደኛውም ክልል እነውክለዋለን የሚሉትን ህዝብ መሰረታዊ ችግሮችን አልፈቱላቸውም። እነዚህን ለመፍታት የሚያስችሉ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመረኮዘ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በየክልሉ በፍጹም አላዋቀሩም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና ማንነቱን እንዲያውቅ የሚያስችሉት ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፉ የትምህርት ተቋማት አልገነቡም።  በተጨማሪም ሊሰራ የሚችል የሰውን ኃይልና ሪሶርሶችን ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ ተቋማትን በፍጹም አልገነቡም። በአጭሩ በጎሳ ፌዴራሊዝም ስም የኋሊት ጎዞ ነው የተደረገው። በመሰረቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም የግለሰብ ነፃነትን፣ የሪፖብሊካን አስተሳሰብንና የህግ-የበላይነትን የሚቀናቀን፣ ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት የሆነ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆነ ጤናማ የሆነውን የህብረተሰብ ኢቮሉሺነራዊ ዕድገት የሚቀናቀን ነው። የወያኔን ወይም የትግሬን የበላይነት ለማስፈን ሲባል በከፋፍለህ ግዛው ስልት ብሄረሰብ የሚባለውን ከዘጠና በላይ የሚሆነውን ህዝብ በአስተሳስቡና በአኗኗሩ ቀጭጮ እንዲቀር ነው ያደረገው። ወደ ጠቅላላው የአገራችን ሁኔታ ስንመጣ ሰፋ ያለ በማኑፋክቸር፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ነው ያደረገው። በመሆኑም በዚህ መልክ የተዋቀረው ስርዓት ለሰፊው ህዝብ የሚሆን የስራ ዕድል ለመክፈት አልቻለም። እንደሚታወቀውና ስለኢኮኖሚ ዕድገት ሀሁ የሚያውቅ ሰው፣ በምርት(Production)፣ በአከፋፈል(Distribution)፣ በንግድ ልውውጥና በፍጆታ(Consumption) መሀከል ዲያሌክታዊ ግኑኘነት አለ። እነዚህ ነገሮች እንደመሰረታዊ ነገሮች ሲወሰዱና ኢኮኖሚውም በዚህ መልክ ሲታቀድ ብቻ ነው ሰለገበያ ኢኮኖሚ መናገር የሚቻለው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የጎሳ ፌዴራሊም ይህንን መሰረታዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ህግ የጣሰና አጠቃላይna ሁለ-ገብ ዕድገት እንዳይመጣ ያገደ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ለመረዳት የየክልሉን ዋና ከተማዎች፣ መንደሮችና የሰፊውን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል።

ጎሳ ወደሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ጋ ልምጣ። በመሰረቱ ጎሳ የሚባል የሰው ልጅ ካለ ከሌላው ጋር ሳይገናኝ በአንድ አካባቢ ተዘግቶ የሚኖር ነው ማለት ነው። በዚህ መልክ የተደራጀ ጎሳ ካለ በመሀከሉ የስራ-ክፍፍል የለም። የአኗኗር ስልቱም በአደንና በከብት እርባታ እየተመካ ነው የሚኖረው። ስለሆነም በዚህ መልክ የተደራጀ ጎሳ ካለ የማደግ ኃይሉ በጣም የመነመነ ነው ማለት ይቻላል። የአንትሮፖሊጂ መጽሀፎችን ላነበበ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ የማሰብ ኃይል ስላለው ከአንድ የአኗኗር ስልት ወደ ተሻለ የማደግ ኃይል ይለወጣል። ለምሳሌ ከፍራፍሬ ለቃሚነትና ከአዳኝነት በመላቀቅ ተቀማጭ በመሆን እያረሰና ከብቶችን እያረባ የተሻለን ኑሮ ይኖራል። በዚህ ብቻ ሳያቆም፣ ሳይወድ በግድ የእርሻ መሳሪያዎችን ስለሚያመርት ቀስ በቀስም የዕደ-ጥበብ ሙያን ይማራል። በዚህ መልክ በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ የስራ-ክፍፍልን በማዳበር በዚያው መጠንም የንግድ ልውውጥ ያደርጋል። ከተማዎችንና መንደሮችን በመገንባት ለመገበያያ የሚሆን አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ቀስ በቀስም ለመገበያያ የሚሆን ገንዘብ ይፈጥራል። ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ በገበያ ላይ ስለሚገናኙ በዚያው መጠንም ቀስ በቀስ ማህበራዊ ባህርይ ያዳብራሉ። በመጋባትም ለየት ያለ ማህበረሰብ ይፈጠራል። በዚህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ሂደት ውስጥ ጎሳ የሚባለው ነገር በመክሰም ሶስዮሎጂያዊ ባህርይ እንዲወስድ ይገደዳል ማለት ነው። ቀስ በቀስም በተለያዩ ሙያዎች በመሰልጠንና የገቢያቸውንም ሁኔታ በማሻሻል እንደመደብ ሊዳብሩ ይችላሉ። ይህም ማለት ግን ርስ በርሳቸው ይጋጫሉ ማለት አይደለም። Income Classes እንዳሉና በተለያዩ የስራ-ክፍፍልም የተሰማሩና፣ በዚህም ራሳቸውንና ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚፈጠሩ ለማሳየት ብቻ ነው። የሚመረቱትም ምርቶች ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ ስለማይሆኑ ምርቶችም እንደየሰው የገቢ ሁኔታ ሁሉንም፣ የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅሙ ናቸው።  ገበያ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያገናኝ እንደመሆኑ መጠን አድልዎ የሚፈጠርበት ሁኔታ አይደለም። ሁሉም በየፊናው ለራሱ ጥቅም ስለሚሯሯጥ ገበያ ላይ ወጥቶ የሚሸጠው ምርት ጎሳዊ ባህርይ የሚኖረው አይሆንም ማለት ነው። ዋናው ነገር ሸጦ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው ዓላማው።

ለምሳሌ በተለይም ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር በደንብ ላጠና ተግባራዊ በሆነው ትምህርት፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የተቋማት ለውጥ፣ አዲስ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን፣ የተዝረከረኩ ቢሆንም የከተማዎች ግንባታ፣ የስራ-ክፍፍል መዳበር፣ በኢኮኖሚውና በንግድ እንቅስቃሴ የተነሳ በሶስይሎጂ አጠራር ህብረተሰቡ እየተለያየና(Social Differentiations)  አንዳንዱም ከተወለደበት ቦታ በመልቀቅ ወደ ሌሎች የተሻለ ዕድል ወደ ሚያገኝባቸው ቦታዎች በመሄድ እዚያው እንዲኖሮ መገደድ የሚያመለክተው የአንድን ህብረተሰብ ውስጣዊ ኃይል ነው። በሶስዮሎጂም በቀጥታና(Vertical) አግድሞሽ(Horizontal) የህብረተሰብ እንቅስቃሴ የሚባል ነገር አለ። በዚህ መልክም ህብረተሰቡ ይቀላቀላል። ስለሆነም ገጠር ውስጥ በግብርና ስራ ወይም በአዳኝነት ወይም በሌላ ስራ ይተዳደር የነበረው ዕድል ያጋጠመው ፋብሪካዎች ውስጥ እየተቀጠረ መስራት ችሏል። ሌላው አይ የሱቅ በደረቴ ነጋዴ በመሆን በዚህ መልክ ኑሮውን ለማሸነፍ የሚሯሯጥ የህብረተሰብ ክፍል ተፈጥሯል። ሌላውና ብልጥ የሆነውና ዕድል ያጋጠመው ደግሞ ከትንሽ ሁኔታ በመነሳት ቀስ በቀስ በንግድ መስክ ውስጥ በመሰማራት ሀብታም ለመሆን የበቃ አለ። ሌላው የመማር ዕድል ያጋጠመው ደግሞ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በተለያዩ መስሪያቤቶች ተቀጥሮ በመስራት ሶስዮሎጂያዊ ባህርይ ለመውሰድ የበቃ አለ። ሰለሆነም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ወደ አገራችን ምድር ሰተት ብሎ የገባው ልዩ ዐይነት የአመራረትና የፍጆታ አጠቃቀም፣ እንዲሁም የአኗኗር ስልት በአንድ ብሄረሰብ ብቻ ሳይወሰን ከተለያዩ ብሄረሰብ የተውጣጡትን በሙሉ ለማዳረስና በባህርያቸውም እንዲለያዩ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ ከኦሮሞ ብሄረሰብ ወጣሁ የሚለውና ሀብታም ለመሆን ዕድል ያጋጠመው አብዛኛውን ጊዜ የሚገናኘው ከአማራ ወይም ከሌላ ብሄረሰብ ተወለድኩ ከሚለውናው ሀብታም ከሆነው ሰው ጋር ነው። ይህም ማለት ሀብታም የመሆን ዕድል ያጋጠመው የኦሮሞ ተወላጅ ነኝ የሚለው ዝቅ በማለት አንድ በሊስትሮነት፣ ወይም በሱቅ አደሬነት፣ ወይም ደግሞ በግብርና ስራ ከሚተዳደረው ጋር በፍጹም አይበላም። ልጆቹንም የሚድረው ከሀብታም ቤተሰብ ለተወለዱ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ ከወጡ ልጆች ነው።  ከዚህ ሁኔታና ከሰው ´ልጅ ውስጣዊና የመንቀሳቀስ ኃይል ስንነሳ በመሰረቱ ጎሳ የሚባለው አጠራር ቦታ የላቸውም። በፍልስፍናም ሆነ በሶስዮሎጂ እንደዚህ ብሎ መጥራት የተለመደ አይደለም። ለምሳሌ ፕሌቶ በግሪክ ዘመን የጎሳ ሶሊዳሪቲና አስተሳሰብ  መኖር የለበትም ብሎ የሚከራከር ነበር። ምክንያቱም የጎሳ ሶሊዳሪቲ የሚባለው አስተሳሰብ ከተፈጠረ ተከታታይነት ያለው ጦርነት መከፈቱ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ለዕውቀትና ራስን በራስ ለማግኘትና እንደሰ ለመኖር እንቅፋት መሆኑን በመረዳቱ ነው። የጎሳ ሶሊዳሪቲ አብዛኛውን ጊዜ ሊጠቅም የሚችለው በደሃው ብሄረሰብ ስም የሚነግድንና፣ ጭንቅላቱን በማስጨነቅ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠርና ለመስራት የማይፈልገውን ኤሊት ብቻ ነው።  ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም ተማርን የሚሉ ወይም ምሁር ነን የሚሉ አንድ ነገር ከማለታቸው ወይም ከመጻፋቸው በፊት የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት አንትሮፖሊጂካል በሆነ መልክ ማጥናት አለባቸው። በተጨማሪም ይህንን ጉዳይ በለጸጉ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ መነጠቁ ከሚባሉ ከካፒታሊስት አገሮች ጋር ማወዳደር አለባቸው። ይህም ማለት አንድ አገር በታቀደ መልክ ከተማዎችን ከገነባ፣ የተጠናና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ተግባራዊ ካደረገ፣ የጥበብና የዕውቀት ማዕከላት በየቦታው ከዘረጋ፣ የሰለጠኑና የተቀላጠፉ ተቋማት በየቦታው ከተገነቡ፣ በተለይም የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት የሚኮተኩቱ ልዩ ልዩ የሙያ ማሰልጠኛ የዕውቀት ዘርፎች ከተስፋፉ፣ በየቦታው የመጻህፍት ቤቶች ከተዘረጉና ወጣቱም የማንበብ ዕድልን ካካበተ የጎሳ ጥያቄ የሚባለው ነገር ቦታ አይኖረውም። ስለሆነም ሁሉንም የማሳስበው የለጠነ አስተሳሰብ እንዲኖረንና የሰለጠነና ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለ ህብረተሰብ እንድንገነባ ነው። ከዚህ ውስጭ የሚነሱ አላስፈላጊ ነገሮች ህብረተስባችንን ለብዙ መቶ ዓመታት የሚያወዛግቡና ወደ ኋላም ቀጭጮ እንዲቀር የሚያደርጉ ናቸው።

ለማንኛውም በአገራችን ምድር የጎሳን ጥያቄ ያነሱ የተማሪው ማህበር መሪዎችና የኋላ ኋላም ይህንን በመከተል የትግል መመሪያ ያደረጉ ከዚኸኛው ወይም ክዚያኛው በሄረሰብ ወጣን የሚሉ የመበደልን ወይም የመጨቆንን ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። የጎሳ ጥያቄ በኢትዮጵያ ምድር ብቅ ሊል የቻለው ካፒታሊዝም ባልተስተካከለ መልክ ሲገባ የተዘበራረቁና ያልተሰተካከሉ ሁኔታዎችን(Unequal Development) በመፈጠሩ ብቻ ነው። ለምሳሌ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ሁለ-ገብ የሆነ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ቢተገበር፣ ከተማዎችና መንደሮች በአማረ መልክ ቢገነቡ ኖሮ፣ ከተማዎችና መንደሮችን በተለያዩ የመጓጓዣ ዘዴዎች ቢገናኙ ኖሮ፣ ይህ ሁኔታ ለሰፊው ህዝብ የስራ ዕድል ስለሚከፍት የብሄረሰብ ጥያቄ በፍጹም አይነሳም ነበር። ምክንያቱም በየቦታው የስራ መስክ ስለሚከፈት ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ መጣሁ የሚለው የስራ ዕድል ለማግኘት ሲል ካለበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ የተሻለ ዕድል ለማግኘት ስለሚጥር ነው። የስራ ዕድልም የሚያገኝ ከሆነ የሄደበት ቦታ በመኖር ከሌላ ብሄረሰብ ከመጣች ሴት ወይም ወንድ ጋር በመጋባት ልጆች ይወልዳሉ ማለት ነው። በዚህ መልክ የተቀላቀለና  ውሰጠ-ኃይል ያለው፣ ሊያስብና ለፈጥር የሚችል አዲስ ትውልድ ይፈጠራል ማለት ነው። ይህ ጤናማው የህብረተሰብ ዕድገትና በታሪክና በሳይንስም የተረጋገጠ ነው። በሌላው ወገን ጨቋኝ እየተባለ የሚፈረጀውን የአማራውን የኑሮ ሁኔታና የከተማዎችን ዕድገት ስንመለከት ከሌሎች ክፍለ-ሀገራት ጋር ሲወዳደር እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ነበር ማለት ይቻላል። ስለሆነም ነው በቡና ለቀማ ሰዓት ከጎንደር፣ ከጎጃም፣ ከወሎ፣ አልፎ አልፎም ከትግሬ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ገበሬዎች ስራቸውን እየተዉ ወደ ከፋ፣ ኢሊባቦር፣ ሀረር፣ አርሲና ሲዳሞ ይሰደዱ የነበረው። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ የኢትዮጵያን የሶሽዮ ኢኮኖሚክ አወቃቀር(Socio-economic formation) የተከታተለ ቢሆን ኖሮ በመሰረቱ በአገራችን ምድር የነበረው ችግር የጎሳ ችግር፣ ወይም ጎሳዎች በመጨቆናቸው ሳይሆን አገዛዙ በተከተለው የተሳሳተና ኢሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተፈጠረ ሁኔታ መሆኑን በተረዳ ነበር። ከዚህም በላይ የታዳጊውን ትውልድ መንፈስ በሚገባ የሚያንጽና በሁሉም አቅጣጫ እንዲያስብና ራሱንም እንዲያገኝና የሚሰራውንም እንዲያውቅ የሚያስገነዝበው ሁለ-ገብ የሆነ ትምህርት ቢሰጥ ኖሮ ቀድሞም ሆነ ዛሬ የሚታየው በጎሳ ስም የሚሳበበው ውዝግብ ብቅ ባላለና ህዝባችንን ስቃይ ውስጥ ባልከተተው ነበር። በመሆኑም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንም ዐይነት አማራውን አልጠቀመውም። የኑሮውንም ሁኔታ በፍጹም አላሻሻለለትም። ስልጣን ላይ የነበረውም አገዛዝ ጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚወክል ነበር እንጂ አማራውን የሚወክል አልነበረም። በገዢው መደብ ውስጥም በተለይም ከአማራው፣ ከኦሮሞው፣ ከትግሬና ከኤርትራ፣ እንዲሁም ከሌሎች ብሄረሰቦች የተውጣጡ ይገኙበታል። አፄ ኃይለስላሴም ሆነ በኋላ ላይ ደርግ በመሰረቱ አማራውን ብቻ የሚጠቅም የኢኮኖሚም ሆነ ሌላ ፖሊሲ በፍጹም ተግባራዊ አላደረጉም። የትምህርት ዘርፉም ሆነ የስራ ዕድል ለሁሉም ክፍት ነበር። በእርግጥ በነበረው ድህነትና ኢኮኖሚው በሚገባ ባለመዋቀሩ የተነሳ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተከታታይ ገቢ ስላልነበረውና ከእጅ ወደ አፍ በሚሰራ ሁኔታ ይተዳደር ስለነበር ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ያልቻለ የህብረተሰብ ክፍል ጥቂት ነው አይባልም። ይህ ጉዳይ ግን በማወቅ የተሰራ ሳይሆን የአፄው አገዛዝም ሆነ የደርግ አገዛዝ ስለህብረተሰብ፣ ስለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ አስፈላጊነት፣ ስለከተማዎችና መንደሮች ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባት፣ እነዚህም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች መይያዝ ስላለባቸው ሁኔታ …ወዘተ፣. በዙም የሚያውቁት ነገር ስላልነበረና፣  አብዛኛው ነገር በአቦ ሰጡኝ ይሰራ ስለነበርና ስትራቴጂኪያዊ በሆነ መንገድ ስለማይታሰብ ህዝባችንና አገራችንን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት በፍጹም አልተቻለም። እያንዳንዱም ዜጋ አገሩን አገሬ ብሎ እንዲጠራትና አብሮም እንዲገነባ መሰራት የነበረባቸው ነገሮች ስላልተሰሩ ህዝባችን እንደማህበረሰብ እንዳይተሳሰር ለመሆን በቃ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ላጎበደዱና በገንዘብ ለሚደጎሙ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ ተውጣጣን ለሚሉ የየብሄረሰቡ ተገንጣይና ችግር ፈጣሪ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። የአብዛኛውን የብሄረሰቤን መብት አስጠብቃላሁ፣ ለነፃነትም እታገላለሁ የሚለውን የየብሄረሰቡን ኤሊት ዕውቀትና ጭንቅላት ስንመረምር አብዛኛዎቹ ወይም ሙሉ በሙሉ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት የተካኑ ናቸው ማለት ይቻላል። ስለህብረተሰብ ዕድገትና ሰለአስቸጋሪው ጉዞ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። መንፈሳቸውም ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር የተጣላና ለጠብ የተዘጋጁ ናቸው።  ጭንቅላታቸው በዕውቀት ያለተኮተኮተና ያልዳበር ስለሆነ በአመጽ ብቻ ነው የሚያስቡት። ሎጂካልና ራሽናል በሆነ መንገድ የማሰብ ኃይል የላቸውም። ስለሆነም  አብዛኛዎቹ እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄረሰብ  ከሁለትና ከሶስት መቶ ዓመት በፊት ይኖርበት የነበረበትን ሁኔታ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። ወደ ኋላ በመጓዝ ሁኔታዎችን በማጥናት እንደዚህ ነበር ወይ ብለው በማውጣትና በማውረድ የየብሄረሰባቸውን የአኗኗር ሁኔታ ለመቃኘት አይሞክሩም። በደመ-ነፍስ በመመራትና በውጭ ኃይሎች በመጠምዘዝና በመመራት ችግር ፈጣሪዎች  ለመሆን የበቁ ናቸው። ፀረ-ሳይንስ፣ ፀረ-ጥበብና በጠቅላላው ሲታይ ፀረ-ዕውቀት ኃይሎች ለመሆን የበቁ ናቸው። ባጭሩ የራሳቸውን ዜጋ የተሟላ ዕድገት የሚቀናቀኑ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላውና የጥቁር አፍሪካ ህዝብ ፀሮች ናቸው። ስራቸው ሁሉ ለውጭ ኃይሎች የሆነና፣ የሚያካሄዱትም ጦርነት የውክልና ጦርነት ነው። በአዳዲስ መኪናዎች እየተጓዙ፤ ሱፍ ልብሶችን እየለበሱና ውድ ጫማዎችን በማድረግና በስማርት ፎን በመደወል የሚንደላቀቁ የዘመኑ ሽብር ፈጣሪዎች ናቸው። ለሲቪል ማህበረሰብ ጠንቅ የሆኑና  የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት የሚቀናቀኑ ናቸው።  ሰልሆነም ብሄረሰባቸውን ሊወክሉ የሚችሉ አይደሉም።

ያም ሆነ ይህ ይህ ጉዳይ በአገራችን ምድር በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን ተግባራዊ የሆኑት ነገሮች በሙሉ ሆን ተብለው ሳይሆን ትላንትናም ሆነ ዛሬ የተገለጸለትና ብሄራዊ ባህርይ ያለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ብቻ ነው።  ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ የአውሮፓውን የህብረተሰብ ታሪክ በሚገባ ተከታትሎ  ቢሆን ኖሮ ጎሳና ታሪክ የምርምር ጉዳዮች በፍጹም ሆነው አያውቁም። ከግሪኩ ስልጣኔ ጀምሮ፣ እስከማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ድረስና በኋላም ላይ በአውሮፓ ምድር የምርምር ዋናው መሰረቶችና ጉዳዮች ፍልስፍና፣ ማቲማቲክስ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ አርኪቴከቸር፣ የከተማ ዕቅድ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የኢንዱስትሪ አብዮት ሲካሄድ ኢኮኖሚክስና ሶስዮሎጂ የምርምር ጉዳዮችና ዘዴዎች በመሆን ህብረተሰብአዊ ችግሮችን መፍቻ ዘዴዎች ለመሆን በቁ። በ19ኛው ፍለ-ዘመንና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የስነ-ልቦና ሳይንስ ሊዳብር ቻለ። በግሪክ ፈላስፋዎች ዕምነት መሰረት የሰው ልጅ ሁሉ ችግር ትክክለኛውን ዕውቀት አለማግኘት ስለሆነ የሰውን አስተሳሰብ ራሱን እንዲያገኝና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን እያወጣና እየለወጠ በመጠቀም እንደሰው ሆኖ ሊኖር የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ከሞላ ጎደል የግሪኩና የኋላ ኋላም የአውሮፓ ፈላስፋዎች አካሄድ ትክክለኛውና ሳይንሳዊው መንገድ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የፕሮፌሰር መሳይ ከበደ አካሄድ ወደ ኋላ የሚጎትተን ብቻ ሳይሆን፣ ቀጭጨን በመቅረት በውጭ ኃይሎች እንድንገዛ የሚያደርገን ነው። የፕሮፌሰሩ አገላለጽ ሳይንሳዊ ባህርይ የጎደለውና ማንኛውንም ብሄረሰብ የሚባለውን በምንም ዐይነት ዕወነተኛ ነፃነቱን እንዲጎናጽፍ የሚያስችለው አይደለም። የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት የሚያደናቅፍ ነው። ለዝንተ-ዓለም በብሄረሰብና በሃይማኖት ስም እየተናቆርን እንድንኖር የሚያድረገን ነው። ሰው መሆናችንን እንድነዘነጋ የሚያደርገን ነው። በተጨባጭ ሲታይ መሳይ ከበደና መሰሎቹ ለነጩ የኦሊጋርኪ መደብ ነው የሚሰሩት ማለት ይቻላል።

የፕሮፈሰር መሳይ ከበደ አካሄድና ትንተና በመሰረቱ ሳይንሳዊ ባህርይ የለውም። የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ደረጃ በደረጃ በማጥናት ችግሮችን ለማወቅ የሚረዳ የሚቻልበት አቀራረብ አይደለም። ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ሶስይሎጂያዊ አቀራረብ የሚጠቅመውም በብሄረስብ ስም የሚነግዱና ከዓለም አቀፍ ካፒታሊዝምና ከኤሊቶች ጋር የተቆላለፉ ጥቂት ኃይሎችን ብቻ ነው። በአጭሩ ጦርነትን ቀስቃሾችንና ድህነት እንዲፈለፈል የሚፈልጉ ኃይሎችን ብቻ ነው።  በአገራችን ምድር በብሄረሰብ ስም የሚነግዱ ኤሊቶች ንጹህ በንጹህ ኦሮሞ ነኝ፣ አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ኩሎ ኮንታ ነኝ… ወዘተ. ሊሉ አይችሉም። ለምሳሌ አቢይ አህመድ በእናቱ መርሃቤቴ ሲሆን፣ በአባቱ ደግሞ ትግሬ ወይም አረብ ነው። አጋሮ ስለተወለደና እዚያው ሶሻላይዝድ ስለሆነ የኦሮሞን ስም መጠቅምና የስልጣን መባለጊያ ለማድረግ በቅቷል። እሱ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ግን የሰፊው ኦሮሞ ነኝ የሚለውን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ በፍጹም አልተሻሻለም። ጀዋርም በእናቱ መንዜ ሲሆን፣ አባቱ ደግሞ የመናዊ ነው። እነ ሌንጮ ባቲም ባባታቸው የጎንደር ቄስና በእናታቸው ደግሞ ኦሮሞዎች እንደሆኑ  ይታወቃል። ባለፉት አምስት ዓመታት ተኩል እነዚህ በየብሄረሰባቸው የሚነግዱ የኦሮሞ ኤሊቶች ምንም ነገር ሳፈጥሩና ሳይሰሩ የናጠጡ ሀብታሞች ለመሆን በቅተዋል። ለማንኛውም ኦሮሞና ሌሎች ብሂረሰቦች የባይሎጂ መለያዎች ሳይሆኑ ሶሻል ኮንስትራክሽን ናቸው።  ከሶስትና ከአራት ሺህ ዓመት በፊት ኦሮሞ ወይም ሌላ ጎሳ መኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም። የሰው ልጅም ስልጣኔ ከአስር ሺህ ዓመት ጀምሮ ተቀማጭ በመሆን መሬትን በማረስና ከእርሻ ሙያ ጋር ሲለማመድ የሚገለጽ ነው። በዚያን ጊዜ በተለያየ የመተሪያ ስም የሚጠሩ ብሄረሰቦች ለመኖራቸው ምንም ማስረጃ የለም። የአንትሮፖሎጂም ጥናት የሚያመለከተው የሰውን ልጅ የዕድገት ጉዞ ብቻ ነው።

እንደ ፕሮፈሴር መሳይ ከበደንና ሌሎችን የማሳስበው አላስፈላጊና ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን እያነሳችሁ ሰፊውን ህዝብ ባታሳሳቱት በጣም ጥሩ ነው። ለጭንቅላት መዳበርና ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያስፈልጉ ብዙ የሚሰሩ ስራዎች ስላሉ ጭንቅላትን በሚበክሉና በሚያሳስቱ ነገሮች ላይ ጊዜያችንን ባናባክን ይሻላል።  በአገራችን ምድር የብሄረሰብ ወይም የጎሳ ችግር የለም።  ችግሮች አሉ ከተባለ ጥቂት ኤሊቶች የፈጠሩትና የሚፈጥሩት ነው። ያለው ችግር የኢኮኖሚ ዕድገት ችግር ነው። ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ኢኮኖሚ ዕድገት  ስለሌለ ሌሎች ማህበራዊና የአካባቢ፣ እንዲሁም የባህልና የስነ-ልቦና ቀውሶች ተስፋፍተው ይታያሉ። ይሁንና እነዚህ መሰረታዊ ችግሮች በጎሳ ሰበብ ተሸፍነው ቀርተዋል። ተማርኩ የሚለው በእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ላይ መወያየትና መፍትሄ መፈለግ አልቻለም። የመንግስት መኪናውና የፖለቲካ መስኩ የደንቆሮዎችና የዱርዬዎች መሰብሰቢያ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች በማባባስ ጎሳዊ ባህርይ እንዳላቸው ለማስመሰል እየሞከረ ነው። በአገራችን ምድር አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን እየተካሄደ አገርን በማፈራረስ ላይ ይገኛል። መልካም ግንዛቤ!

                                                                            fekadubekele@gmx.de

                                                                                               www.fekadubekele.com