[gtranslate]

የምንፈልጋቸው ነገሮች ነገር ግን ደግሞ ሂደታቸው የጨለሙብን !!

ግልጽ መሆን ያለባቸው መሰረተ-ሃሳቦች!!

                                                                                                                                                                                                                                                                                                   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                                                                                                                                                                                                                                              መስከረም 20፣ 2017              

መግቢያ

        ከረዥም ዓመታት ጀምሮ ሃገራችንን የተናወጧት ሁለት እንደ ነቀርሳ በሸታ የሚሰረስሯትና ህልውናዋን ያዳከሟት ነገሮች በግልጽ ይታያሉ። አንደኛው ራሱ ታጋይ ነኝ የሚለው ምሁር መፍትሄ ፈላጊ መሆኑ ቀርቶ ችግር ፈጣሪ መሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ምሁሩ በሚፈልገውና በሚከተለው የትግል ስልት ዘንድ ያለመጣጣም መኖሩ። በፕሪንስፕል ደረጃ መከተል ባለብን መሰረተ-ሃሳቦች ዘንድና እንደ ዐላማ ለመድረስ በምንፈልጋቸው ነገሮች  ለመጣጣም የማይችሉ ሁኔታዎች ተፈጥረው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የዋህ ህዝቦችን እያምታቱ ይገኛሉ። ሰላም የሰፈነባትን፣ የበለጸገችና የተከበረች እንዲሁም ደግሞ ህዝቦቿ ሙሉ ነጻነቷን ተቀዳጅተው በመፈቃቀርና በመከባበር የሚኖሩባት ሃገር መመስረት ከተፈለገ ደግሞ ማንኛውም ምሁር ነኝ የሚል ሊከተላቸው የሚገባቸው መስረተ-ሃሳቦችና እሴቶች አሉ። ከመሰረተ-ሃሳብና ከእሴት ውጭ የሚደረጉ ዕቅደ-አልባ አካሄዶች የመጨረሻ መጨረሻ በታኝ እንደሚሆኑ ከብዙ ሃገሮች ታሪክ የምንቀስመው ልምድ  ነው።

        አንድ በኛ ምሁሮች ዘንድ በፍጹም ከሰውነታችን ጋር ሊዋሃድ የማይችል ትልቅ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ሲያስጨንቀንና ወደ ፊት አላራምድ ብሎ ሲያንገዳግደን ይታያል ። ይኸውም ለሚከሰቱ ወይም አፍጠው አግጠው ለሚታዩ ችግሮች ጥያቄ በመጠየቅ መፍትሄ ለመስጠት ያለመቻል። እንደሚታወቀው ማንኛውም ችግር ሊከሰት የሚችለው ካለበቂ ምክንያት አይደለም። ስለዚህም ይላል ላይብኒዝ፣ ለማንኛውም ሁኔታ ወይንም ነገር መፈጠር የግዴታ በቂ ምክንያት አለ። ራሱ እንደሰው ለመፈጠራችን በቂ ምክንያት አለን። እንዲሁም ለምን በዚህች ፕላኔት ላይ ብቻ መኖር እንዳለብን በቂ ምክንያት አለ። ስለዚህም፣ በዚህች ሁሉ ነገር ተመቻችቶ በተሰጠን ፕላኔት ውስጥ ስንኖር የምንሰራቸው ስራዎችና የምንከተላቸው መሰረተ-ሃሳቦች በአቦ ሰጠኝ ሊሆኑ በፍጹም አይገባቸውም። ትግል እንበለው የኑሮ ስልት ሳይንሳዊውን መንገድ ይዞ የማይጓዙና ከሳይንስም ተነስቶ የማይነደፍ ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ይህ ዓይነቱ የትግል ስልት እጅግ የተዘበራረቀና በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው ሁኔታ ውስጥ ይከተናል።

       ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ከየዋሁ ህዝባችን ዘንድ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ። ይኸውም ልጆቻችንን ትምህርት ቤት የላክናቸው ተምረው፣ አውቀውና ተራቀው ለችግራችን መፍትሄ በመስጠት ታሪክ የሚሰራባትን የተከበረች ሃገር ለመፍጠር ነው። እነሱ ግን በዚህ ፈንታ በሆነው ባልሆነው መናቆርና ወደ ጠብ ማምራትና የባሰውኑ እኛን ወደ ችግር ውስጥ መክተት ነው የሚል ነው። በተጨማሪም የዚህ ወይም የዚያኛው ኃያል መንግስት አፈ-ቀላጤና ተቀጥያ በመሆን የነሱ ተገዢ ሆነን ተዋርደን እንድንኖር ማድረግ ነው የተያዘው ሙያ፤ ታዲያ የትምህርት ዐላማው እንደዚህ ከሆነ ልፋታችን ምኑ ላይ ነው የሚል ትክክለኛ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይሰማል።

      ከዚህ እጅግ መሰረታዊ ጥያቄ ስንነሳ በጭንቅላቴ ውስጥ ከአስር ዐመታት ጀምሮ የሚመላለስና የሚከነክነኝ ነገር አለ። ከዚህ ቀደም ለንባብ ያቀረብኩት ጽሁፍ „ ማየት የማይችል አእምሮ…“ እንዳለ ሆኖ፣ የምንታገልበት የትግል ዘዴ መሰረተ-ሃሳብና ዋና ዓላማ በፍጹም ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም እሱን የሚጋጭና የመጨረሻ መጨረሻም ተበታትነን እንደንቀር የሚያደርገን ፕሪንስፕልስ የሌለው የትግል ዘዴ ነው ብል እንደስድብ አይቆጠርብኝም ። ለዚህ ደግሞ የኛን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች አግጠው አፍጠው የሚታዩትን ችግሮች ለተመለከተና ላጠና የችግሮቹ ዋና ምንጭ ሳይንሰ-አልባ የአስተዳደርና የአኗኗር ስልቶች እንደሆኑ ካለብዙ ጭንቀት መረዳት ይቻላል። በተጨማሪም፣ የብዙ አገሮች መሪዎች ባህርይና የአሰራር ልምድ ከዕውነተኛ የጭንቅላት ነፃነትና  ዲሞክራሲያዊ ባህል ጋር የተዋሃደ ባለመሆኑ ምስኪን ህዝቦች ከእንስሳ እኩል እንኳ መቆጠር የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ወድቀው ሲሰቃዩ በየዕለቱ የምናየው ሀቅ ነው። በየአገሩ በምርጫም ሆነ በጉልበት ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያሉ መሪዎች በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠሩ ህዝቦችን የመኖር ዕድል በመወሰን አብዛኛውን ህዝብ ወደ ባሰ ችግርና ጦርነት ውስጥ እየከተቱት መጥተዋል። እንደዚህ ዐይነቱ የአገዛዝ ስልት ተፈጥሮአዊ ተደርጎ በመወሰዱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጥሩ ህዝቦች ነፃነታቸውን ተገፍፈው፣ የሚፈጸምባቸውን የአገዛዝ ግፍ ለመቃወም ሲነሱ መልሱ መገረፍ፣ መታሰርና መገደል ሆኗል። እንደዚህ ዐይነቱም በደል በአገራችን ውስጥ በመስፋፋቱ ህዝባችን ዕውነተኛ ታሪክ እንዳይሰራ ተደርጎ ሊወጣው የማይችለው አስቸጋሪ ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ሲሰቃይ እንዲኖር ተገዷል። ረሃብ፣ ድህነትና መሰደደ ዕጣው ብቻ ሳይሆን፣ ባህሉ ሆኗል ማለት ይቻላል። ጥቂት ተምረናል የሚሉና ብልጣ ብልጥነት የሚያጠቃቸው ባገኙት ጊዜያዊ ኃይል በመጠቀምና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር፣ በሳይንስ ያልተደገፈ ፖሊሲ በማውጣት የህዝቡ አስተሳሰብ ተበታትኖና ምስኪን ሆኖ እንዲቀር አድርገውታል። የህዝባችን ሃሳብ መበታተንና አቅሙ መዳከም የአገዛዙ ጥፋት ብቻ አይደለም። ራሱ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ይህንን ከረዢም ጊዜ ጀምሮ የተደገሰለትን ድግስ ጠጋ ብሎ ለማየትና ለመከላከል ባለመቻሉ ለአገራችን መዋረድ የበኩሉን አስተዋፅዎ አድርጓል። እያደረገም ነው። እስካሁን እንደታየው፣ በራሱ ላይ ዕምነት ኑሮት በሚያምንበት ፍልስፍና በመመራትና በማስተማር ህዝባችንና አገራችንን ከገቡበት ማጥ ውስጥ ለማውጣትና አዲስ ህይወት ለመስጠት የተዘጋጀ አይመስልም። በራሱ ላይ ከመተማመን ይልቅ በውጭ ኃይሎች ቡራኬ ነፃነት የሚገኝ እየመሰለው አንዳች ነገር በመጠባበቅ ላይ ያለ ይመስላል። ይህ ዐይነቱ ችግር ሊኖር የቻለው እስከዛሬ ድረስ ተቃዋሚው ኃይል አንዳች ነገር ቢፈልግ እንኳ የሚፈልገውን ግልጽ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን ወደዚያ ለማምራት መከተል ያለበትን የትግል ስልት ለማሳየት ያለመቻሉ ነው።

       የዚህ ጽሁፍ መሰረተ-ሃሳብ ይህንን ለመዘርዘርም ሆነ ለመተቸት አይደለም። የዚህ ጽሁፍ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ እስከዛሬ የምንመራበት የትግል ስልትም ሆነ ልንደረስበት የምንፈልገው ዓላማ ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም ብቻ ሳይሆን፣ ማንም ሰው ሊረዳው የሚችለውንና ሊከተለው የሚገባውን ኮመን ሴንስ(common sense) የትግል መሰረተ-ሃሳብ እንኳ የተመረኮዘ ያለመሆኑን ለማመልከትና፣ በጸሀፊው ዕምነት ዓላማን የተከተለ የትግል ስልት ምን እንደሚመስል ለማመልከት ነው። በዚህም ምክንያት በመሀከላችን ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ሲያናቁረን ይገኛል። በዚህ ፀረ-ሳይንስና ዓላማው ምን እንደሆነ በማይታወቅ የትግል ስልት ግራ በመጋባት ብዞዎች ተስፋ እየቆረጡ እጃቸውን አጣጥፈው ሲቀመጡ ፣ ሜዳው የተለቀቀላቸው ደግሞ እጅግ ወደ ኋላ በቀረ የትግል ስልት በመጠመድና ሌላውን በማደንቆር ለሌላ የርስ በርስ ጦርነት እየጋበዙት ነው። የዛሬው የትግላችን ችግር በአገራችን ምድር በስልጣን ላይ ተንሰራፎ የተቀመጠውን አደገኛና አገር አጥፊ አገዛዝ ባህርይና ሚናውን የመረዳት ጉዳይ አይደለም። የዛሬው ችግር የኛን ፀረ-ሳይንሳዊ ትግልና እንደገለሰብም ሆነ በደርጅት ዙሪያ ተሰብስበን ማድረግ የሚገባንን ታሪካዊ አስተዋፅኦ ለመረዳት ያለመቻል ነው። የዚህ ዋናው ችግር ደግሞ በሳይንስ ላይ ያለተመሰረተ የዘልማድ ትግል ከደማችን ጋር መዋሃዱና በዚህ ፈለግ ካለምንም ጥያቄ ወደ ፊት መሸምጠጥ እንደዋናው የትግል ስልት ሆኖ መያዙ ነው። በዚህ ከቀጠልን ደግሞ በሚቀጥለው መቶ ዐመትም ህዝባችን የሚመኘውን የሰላም፣ የብልጽግናና የዲሞክራሲ ኑሮ ለመመስረት በፍጹም አይችልም ማለት ነው ። ትግላችን መልክና ዓላማ እንዲኖረው ከተፈለገ የግዴታ ሳይንሳዊ መስመር መያዝ ሲገባው፣ ዐላማችንን ግልጽ ማድረግ አለብን። ይህ ሲሆን ብቻ አለመግባባትን አስወግዶ የትግሉን ሂደት ማሳጠርና ወደሚያሰፈልገው የስልጣኔ ተግባር ማምራት ይቻላል። ስለሆነም ሳይንሳዊ ትግል ማለት ምን ማለት ነው? ከሚለው በመነሳት በምን በምን መሰረተ-ሃሳቦች ላይ ማትኮር እንዳለብን ለማመልከት እሞክራለሁ። በመጀመሪያ እስቲ ብዙ የሚያጨቃጭቁንን ነገሮች እያነሳን እንወያይ።

በዕውቀት ዙሪያ የሚነሱ ንትርኮች !!

        በእኛ ኢትዮጵያውያኖች ዘንድ የግራንም ሆነ የቀኝን መስመር እንከተላለን በምንለው (ግራና ቀኝ የሚለው የትግል ስልት በብዞዎቹ ታጋይ ነን በሚሉት ዘንድ የቲዎሪው መስረት ምን እንደሆን በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም) ዘንድ ያለው አመለካከት፣ ዕውቀት የሚባለው አንድ ወጥ እንደሆነና በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥም ዕውቀትንና ስልጣኔን በሚመለከት ትግሎች እንዳልተካሄዱ ነው። ስለዚህም ተማረ የተባለው በሙሉ አንድ አመለካከት እንዳለውና አንድን ሁኔታ በአንድ መነፅር ወይም የአገመጋገም ስልት ብቻ ለመተንተን እንደሚችል አድርጎ ነው የሚወሰደው። ከዚህም ስንነሳ ኢኮኖሚክሰ ወይም ደግሞ ሌላ የህብረተሰብ ሳይንስን የተማረ ሁሉ በአንድ ስልት ብቻ የኢኮኖሚ ሄደቶችንና የህብረተሰብ ዕድገትን መገምገም እንደሚቻል ነው ካለምንም ጥያቄ ግንዛቤ ውስጥ የተገባው። ይህ ደግሞ የሚያመለክተው አንድ ህብረተሰብ አንድ ወጥ እንደሆነና በአንድ ፍልስፍና ብቻ እንደሚመራ ተደርጎ በብዝዎቻችን ዘንድ የታመነበት። የህብረተሰብን ታሪክና የተመራማሪዎችን ጽሁፍ ላገላበጠ ደግሞ በታሪክ ውስጥ አንድ ወጥ አመለካከትና አንድ ወጥ ህብረተሰብ እንዳልነበረና ሊኖርም እንደማይችል መገንዘብ ይቻላል።

        የታሪክን ማህደር ላገላበጠ ቢያንስ ሁለት የአመለካከት ስልቶች ሲኖሩ፣ ትክክለኛው ዕውቀት ጋ ለመድረስ ምሁሮች እንደዝንባሌያቸውና በነበራቸው የህብረተስብ ቦታ    አንድን ነገር ወይም የህብረተሰብአቸውን ችግር በአንድ የአመለካከት ዘዴ ብቻ ሳይሆን፣  በልዩ ልዩ ስልት እየነጣጠሉ መገምገምና ለችግሩ መፍትሄም አንድ መንገድ ብቻ ያለመኖሩን በማመልከት ሲያከራክር የቆየና ወደ ፊትም የሚያከራክር ጉዳይ ነው። ከዛሬ ሶስት ሺህ ዐመት ጀምሮ የሰውን ልጅ ሚናና የተፈጥሮን ህግጋት በፍልስፍና መነጽር ለመመርመር ሙከራ ሲደረግ በጊዜው የነበሩትና ኋላም የተነሱት ፈላስፋዎች ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ሚና በአንድ የፍልስፍና ወይም የዕውቀት ዘይቤ መተንተን እንደማይቻል ነው ያረጋገጡት። ስለዚህም ነው ማርክስ አንድ ቦታ ላይ እንደዚህ ያለው፤„ፈላስፋዎች ዓለምን በተለያየ መልክ ገልጸዋታል፤ ቁም ነገሩ ግን መፍትሄውን መሻት ነው“። ይሁንና አንድን ተጨባጭ ሁኔታ የመገምገሙ ጉዳይ የአመለካከት ብቻ ሳይሆን የየፈላስፋዎችንም በህብረተሰባቸው ውስጥ የነበራቸውን ቦታ ያረጋግጣል። በተጨማሪም፣ በዕውቀት አቀሳሰምና የአጠቃቀም ዘይቤ ውስጥ ሞራልና ስነ-ምግባር ዐይነተኛ ቦታን ይጫወታሉ። በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ በተለይም ርዕዮተ-ዓለም መሰረታዊ ቦታ ባለው ህብረተሰብ ውስጥ ስነ-ምግባርና ሞራል ከፍተኛ ቦታ አላቸው። የነዚህ ሁለት ጽንሰ-ሀሳቦችም ትርጉም እንደየግለሰቡ የህብረተሰብ ቦታና ሚና(Social Status) ይወሰናሉ። ስለዚህም ነው በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ የሰብአዊነት ትምህርትና ሌሎችም የትምህርት ዐይነቶች እንደ መመሪያ በመሰጠት ግለሰቦች እንደ የዝንባሌያቸው ይህኛውን ወይም ያኛውን የዕውቀት ዘርፍ በመከተል ህብረተሰባቸውንም ሆነ ራሳቸውን ለመጥቀም ይታገሉ የነበረው። በሌላ ወገን ግን የተለያዩ ፈለስፋዎች ዓለምን በተለያየ መልክ ቢተረጉሟትም ይህ ማለት ግን የሁሉም አተረጓጎም ትክክል ነው ማለት አይደለም። ወይም ደግሞ የተለያዩ አተረጓጎሞች አንድን ህብረተሰብ የግዴታ ታሪክ እንዲሰራና የተረጋጋ ህብረተሰብ እንዲመሰርት ሊያደርጉት ይችላሉ ማለት አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ዕውቀት በተለያየ መልክ ቢተረጎምም አንድ ዕውነት ብቻ ነው ሊኖር የሚችለው እንጂ ብዙ ዕውነቶች በፍጹም ሊኖሩ አይችሉም። እዚህ ላይ ነው የማርክስ አባባል፣ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የሚለው የማይሰራው። ምክንያቱም አንድን ህብረተሰብ በተለያየ መልክ ከተተረጎመና ሁሉም ትክክል ነው ብሎ የሚያምንበትን ሃሳብ ይዞ ከቀረበ አንድ ሊያሰራ የሚችል አቋም ላይ መድረስ በፍጹም አይቻልም። አንድን ነገር በመረዳትና አንድን ህብረተሰብ በመተርጎም መሀከል ልዩነት ቢኖርም፣ በትክክለኛ የሳይንስ መነፅር ከታየ ግን ወደ ዕውነተኛው መንገድ ሊያደርስን የሚችለው አንደኛው የአተረጓጎም ዘዴ ብቻ ነው። አንድን ድልድይ በተለያየ ዘዴና መልክ መስራት ቢቻልም አንድን ህብረተሰብ ግን እንደፈለጉ በመተርጎም የተለያየ መፍትሄ መስጠት አይቻልም። ከተጨባጩ የድልድይ ስራ ሰንነሳ፣ የጥንካሬውን፣ የስፋቱንና የዕድሜውን እንዲሁም የውበቱን(aesthetic) ጉዳይ ትተን ወደ ህብረተሰብ ስንመጣ ብዙ የሚያከራክሩ ጉዳዮች አሉ። ምክንያቱም አንድ ህብረተሰብ በተወሰነ የአለካክ ዘዴ ተለክቶ የሚገነባ ሳይሆን ከብዙ ሁኔታዎች አንፃር መታየት ያለበትና እየተገመገመም መገንባት ያለበት በመሆኑ ነው። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ማቴሪያላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም እንደመሆኑ መጠን ድርጊቱና ህብረተሰብአዊ አስተዋጽዎው ሊወሰን የሚችለው በአካላዊው ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በአካባተው ዕውቀትም ጭምር ነው። ይህ ደግሞ ሊወሰን የሚችለው የየግለሰቡ የዕውቀት መሰረት፣ ተፈጥሮንና የራሱን ሚና ተገንዝቦ ህብረተሰቡን ጥበባዊ በሆነ መልክ ለመለወጥ ነው ወይስ በራሱ ጥቅም ብቻ ታውሮ ወደ ፊት በመሸምጠጥ ግለሰቦች ተፋጠውና ህብረተሰቡ በአጠቃላይ ተዝረክረኮ እንዲኖር እዚህና እዚያ በመዝለል የበላይነቱን ለማሳየት ነው የተማረው የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ በማንሳትም ጭምር ነው። ከዚህ ስንነሳ አንድን ህብረተሰብ በተወሰኑ መሰረተ-ሃሳቦችና እሴቶች ላይ የመገንባቱና በህብረተሰቡ ውስጥም ስምምነት ኑሮ ግለሰብአዊ ጥቅምን ከህብረተሰባዊ ጥቅም ጋር ማጣመር ታሪክን መስራት አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የሚከተለው ዕውቀት መሰረታዊ ቦታን ይይዛል። ዕውቀቱ የተዛነፈና በርዕዮተ-ዓለም የተሸፈነና የጥቂት ሰዎችን ጥቅም ማስጠበቂያ ከሆነ ደግሞ  ህብረተሰቡ ለማኝና ተዝረክርኮም እንዲኖር የሚገደድበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም አንድ ህብረተሰብ ስርዐተ-አልባ ሆኖና ተፈጥሮን እየተቃረኑ የመኖርም ጉዳይ ወይም ደግሞ የተፈጥሮን ህግጋት በመረዳት ሰርዓት ያለው ህብረተሰብ የመመስረቱ ጉዳይ በደፈናው የሁሉም የምሁራን ሚና ሳይሆን፣ በጥቂ ምሁራን ዘንድ በሚካሄድ የጦፈ የአመለካከት ትግልና አንደኛው አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ነው ሊወሰን የሚችለው። ምክንያቱም በተለይም በአሁኑ ዘመን እንዳለ ምሁር የሚባለው ሁሉ በፖለቲካ ትግል ወስጥ የሚሳተፍ ባለመሆኑ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በጣም ጥቂቱ ካልሆነ በስተቀር ይኸኛውም ሆነ ያኛው የምሁር ክፍል ሳይወድ በግድ አንድ የፖለቲካ አመለካከት እንዲይዝ ይገደዳል። ስለዚህም አብዛኛውን ጊዜ አንድን ህብረተሰብ የመምራት ጉዳይ በጥቂት ምሁሮች ትከሻ ላይ ነው የሚወድቀው። ከዚህም ስንነሳ ዛሬ በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ካለምንም ምርምር የተማሩ ይምሩን እያለ የሚያቀርበው ጥያቄና ጩኸት መሰረተ-ቢስ ነው። በሌላ አነጋገር አንድ ህብረተሰብ ከፍተኛ እሴታዊና የርዕዮተ-ዓለም ትግል የሚካሄድበት መድረክ እንደመሆኑ መጠን ጠቅላላውን ምሁር አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት እንዳለው አድርጎ መወሰድ በፍጹም አይቻልም። ከሳይንስም አንፃር ስህተት ብቻ ሳይሆን አንድን ህብረተሰብ ገደል ውስጥ የሚከት አደገኛ አዝማሚያ ነው። ይሁንና ግን ሁሉም ምሁር ለጊዜውም ቢሆን አንድ ዐይነት አመለካከት ቢይዝ ትግሉን የሚያግዝ እንጂ እስከዚህም የሚጎዳ አይሆንም።

       የኛ ኢትዮጵያውያኖች ችግር ከላይ የተዘረዘረውን መሰረተ-ሀሳብ ለመረዳት ያለመፈለግ ወይም ያለመቻል ሲሆን፣ በተለይም በአንድ ህብረተሰብ አገነባብ ውስጥ አእምሮ በትክክለኛ ዕውቀት መታነጽ የሚኖረውን ከፍተኛ ቦታ ቁም ነገር ውስጥ ለማስቀመጥ ብዘዎቻችን አንቃጣም። በዕውቀትና በህብረተሰብ አገነባብ ዙሪያ የተደረገውን ትግል ለተመለከተና የታሪክንም ማህደር ላገላበጠና ዛሬም በጦፈ መልክ የሚካሄደውን ትግል በጥብቅ ለተከታተለ ደግሞ፣ ከሶስት ሺህ ዐመት በፊት የዕውቀትን መሰረት የጣሉ ምሁራን አጥብቀው ያነሱትና ያስተማሩት ጉይ መንፈስ ወይም አእምሮ ወይም ደግሞ ቆንጆ ወይም መጥፎ መንፈስ በህብረሰብ አገነባብ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና አጥብቀው በማንሳት ነው። ስለዚህም የግሪክን ተመራማሪዎችንም ሆነ በሬናሳንስ ዘመንና በኋላ የተነሱትን ምሁራን ጽሁፍ ላገላበጠ፣ ትግሉ የሰውን ልጅ ጭንቅላት በመጥፎም ሆነ በጥሩ መልክ በመቅረጽ ዙሪያ የተደረገ ትግልና የሚሸከረከርም ነው። ዕውቀትን ትተን ሃይማኖትናና ሌሎችንም የአምልኮ ጉዳይች ስንመለከት ማንኛውም ግለስብ መንፈሳዊም እንደመሆኑ መጠን፣ አንድን ነገር አምኖ ከተቀበለ  ካለብዙ ጭንቀትና ምርምር በዕምነቱ እንደሚገፋበት ነው። የሰው ልጅ ማንነቱንና ድርጊቱን እንደሁም ታሪካዊ ስራውን ሊገነዘብ የሚችለው ከብዙ የጭንቅላት ምርምር ብቻ እንደሆነ የሶክራትስንና ከዚያም በኋላ የተነሱትን ምሁራን እጅግ ጠቃሚ መላልሶ ጥያቄን የማቅረብ የትምህርት ዘዴ ላገላበጠ መረዳት ይቻላል።

        ወደ ሌላ ትርጉምና ጭቅጭቅ ውስጥ እንዳንገባ እስቲ ሀቀኛ(authentic) ወደ ምንላቸው መሰረተ-ሃሳቦችና ውይይቶች እናምራ። ለምሳሌ ፕላቶ በሶክራትስ መሰረተ-ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ስለ ዕውቀት የሚለውን እንስማ። ፕላቶንም ሆነ ሶክራተስ የክርክር ወይም አንድን ነገር ጥያቄ ውስጥ የማስገባት ነገር መሰረት አድረገው የሚነሱት ከነሱ ቀደም ብለው የተነሱትን ፈላስፋዎችና ትምህርታቸውን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ነው። የመጀመሪያዎቹ ፈላስፋዎችም የተፈጥሮ ፈላስፋዎች ተብለው ሲታወቁ፣ ፕላቶ ቲዬቴቱስ ተብሎ በሚታወቀውና ስለ ዕውቀት በጻፈው ውስጥ በጥያቄ የሚያስቀምጠው መሰረተ-ሃሳብ፣ ፕሮታጎራስ ተብሎ በሚታወቀው የተፈጥሮ ፈላስፋ የተሰነዘረውን የዕውቀት መነሻ በመቃወም ነው። ፕሮታጎራስ በግልጽ የምናያቸው ነገሮች (sense perception)የዕውቀት መነሻዎች ናቸው፤ ስለዚህም ማንኛውም ነገር ተለዋዋጭና እንደፈሳሽ ነው ብሎ ሲያስተምር፣ ፕላቶ ግን ይህንን በመጻረር ዕውቀት ሊለዋወጥና ስህተትም ሊሆን እንደማይችል በፕርንሲፕል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያስተምራል። ስለዚህም ይላል፣ ዕውቀት አንደኛ፣ ስህተት ሊሆን እንደማይችል ወይም ደግሞ ስህተት የማያሰራ(infallible)፣ ሁለተኛ ደግሞ ስለ ዕውቀት በሚወራበት ጊዜ ስለምንድ ነው (of what is) ብሎ መጠየቅ እንደሚያሰፈልግ ያስተምራል። ስለዚህም በግልጽ የምናየው ወይም የምናያቸው ነገሮች ከሁለቱም አንዱም አይደሉም። ይህንን ለማረጋገጥ ሶክራተስ ተማሪውን ቴዬቴቱስን ዕውቀት ምንድ ነው? ብሎ ይጥይቀዋል። ቴዬቴቱስም ጂኦሜትሪ፣ ሳይንስና የመለኪያም መመሪያ ነው ብሎ ሲመልስለት፣ ሶክራተስ ግን በዚህ ባለመርካት ዕውቀት ስለምንድነው ብሎ አለመጠየቁን በማመልከት፣ ዕውቀት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲያሰረዳው እንደገና ይጠይቀዋል። ስለዚህም የጥያቄው ባህርይ የዕውቀትን መነሻ ማስረዳትና ይህም የተፈጥሮን ውስጣዊ ይዘት ወይም አፈጣጠር እንድንመራመር የሚያደርግ መሆኑን ያስተምራል። ስለዚህም ስለ ዕውቀት በሚወራበት ጊዜ ስለአንድ ነገርና ዕውቀትም ከአንድ ነገር ጋር የተያያዘ መሆኑን ያስገነዝበናል። በመሆኑም ዕውቀት በምናያቸውና በተለዋዋጭ ነገሮች ላይ የተመሰረተ ከሆነ እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ግምት በመስጠት እንደፈለገ ይጋልባል ማለት ነው። ስለዚህም ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ከተቀረጸ ግለሰቦች ይህንንም ሆነ ያንን በመያዝ በፕሪንስፕል ላይ ባለመመርኮዝ አንድን ህብረተሰብ እንደፈለጉት ሊበውዙትና የኑሮውንም አቅጣጫ ሊያዛንፉበት ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ይላል፣ ዕውቀት በግልጽ ከምናያቸው ነገሮች ጋር ከተያያዘና ይኸኛው የዕውቀት መሰረት ከሆነ፣ አንደኛው ሰው ከሌላው ብልህ ወይም አዋቂ ሆኖ ሊገኝ አይችልም ይላል። በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ብሎ በመውሰድና ራሱን መለኪያ አድርጎ በመቁጠር የዕወቀትን ትርጉም ሊያዛንፍ ይችላል። ስለዚህም አንድን ነገር በማየትና ያንን ነገር በማወቅ መሀከል ትልቅ ልዩነት አለ። ለምሳሌ፣ አንድ ጠረቤዛ ስናይ ጠረቤዛ መሆኑን እንገነዘባለን። ከዚያ ገፍተን ግን ብዙም ጥያቄ የማናቀርብ ብዙዎች ነን። ለምሳሌ ጠረቤዛ ጠረቤዛ ከመሆኑ በፊት የተጓዘባቸውን ሄደቶች እንመልከት። በመጀመሪያ ማንኛውም ዛፍ ጠረቤዛ ለመስራት አያገለግልም። ይህ የመጀመሪያው መስረተ-ሃሳብ ሲሆን፣ አንድን ለጠረቤዛ መስሪያ የሚያገለግልን ዛፍ ብንወስድ፣ ዛፉ እንደዛፍ ለማደግ የወሰደበትን እድሜ፣ ለማደግ የተጠቀመባቸውን ንጥረ-ነገሮችና ውሃ፣ እንዲሁም ፀሀይ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ሰው እምብዛም አይደለም። ዛፉ ከተቆረጠ በኋላ ለመድረቅ የሚፈጅበትን ጊዜ፣ ተሰንጥቆና ተልጎ እንዲሁም ለስልሶ ጠረቤዛ ለመስራት የሚወስደውን ጊዜና የሰውም ሆነ በረቀቀ መልክ በጠረቤዛው ውስጥ የሚገባውን ኃይልና ዕውቀት ሊመራመር የሚቃጣ ይህን ያህልም አይደለም። ከዚያም አልፎ በመሄድ፣ አንድ ጠረቤዛ ሲሰራ የብዙ ሰዎች ውጤትና ከብዙ ነገሮችም ጋር በጥብቅ እንደተያያዘ የሚገምት የለም። ዋናው ነገር በግልጽ የምናየው ጠረቤዛ ጠረቤዛ መሆኑንና ለዚህም ወይም ለዚያኛው ነገር ለመጠቀሚያ የገዛነው መሆኑን ብቻ ነው የምንረዳው። ይህ አንደኛው የዕውቀት የተዘናበለ አመለካከት ሲሆን፣ አንድ ዛፍ ተቆርጦ ወደጠረቤዛነት ሲለወጥ፣ የዛፍ መቆረጥ በአካባቢው የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤትና የዛፍ መቆረጥ የግዴታ ከሆነ ደግሞ ያንን ለመተካት ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ጥያቄ ውስጥ የማናስገባ ብዙዎች ነን። ይህ ቀን በቀን በምናደርገውና በምናየው ነገር ውስጥ ብዙም አርቀን ማየት ወይም ጥያቄ ለመጠየቅ እንደማንሞክር ለማሳየት ቢሆንም፣ ይህ ስለ ዕውቀት ብዙም ይነግረናል ማለት አይደለም። በሌላ ወገን ግን እንደዚህ እያለን ማሰብ ስንጀምር ጠለቅ ወዳለ አስተሳሰብ ማምራት እንችላለን። የተፈጥሮን ህግጋት በመመራመር ተፈጥሮን ወደ መኮረጅ ማምራት እንችላለን ። ይህንን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ወደ ሆነ ሶክራትስያዊ የአስተሳሰብ ዘዴ ወደ ኋላ መለስ ብለን እንመልከት። አምስት ሰዎች እንደ ህብረተሰብና አስተዳደግ ዝንባሌያቸው ለአንድ ነገር የተለያየ ትርጉም እንደሰጡትና ለምን ይህ መጨረሻ ላይ ትክክል እንዳልሆነ ሶክራተስ ሲምፖዚየም በሚባለው ግብዣ ላይ ሲያስረዳ እንመልከት።

         ፌድሮስፓውዛኒያስ፣ሀኪሙ ኤሪክሲማሆስ፣ ቀልድ ገጣሚ የሆነው አሪስቶፋኖስ፣ አጋቶን በሚባለው ሰው ቤት ለግብዣ ተጥርተው ስለ ኤሮስ(Eros) ምንነት ይወያያሉ። በግብዣውም ላይ ሶክራተስ ነበር። የመጀመሪያው ተናጋሪ ፌድሮስ፣ ኤሮስ ወይም ፍቅር ማለት መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው እግዚአብሄር ሲሆን፣ የነገሮች ሁሉ መነሻ ወይም ፈጣሪ ነው ብሎ ለተሰበሰበው ያስረዳል። ስለዚህም፣ ይህ ኤሮስ ፍቅረኛሞችን ሀፍረታቸውን በመግፈፍ ታታሪ እንዲሆኑና ቆራጥም ሆነው መሰዋዕትነትን እንዲከፍሉ ለማድረግ የሚችል ነው ብሎ ንግግሩን ይደመድማል። በዚህ ያልተደሰተው ፓውዛኒያስፌድሮስ ነገሩን ለያይቶ ማየት እንዳልቻለና በደፈናው እንደተናገረ ንግግሩን ይጀምራል። የሰማዩ እግዚአብሄር ከመንፈስ ርቆ በመሄድ ሰውነታዊ ሰሜቱን ለማርካት በህብረተሰብ ውስጥም የሚነቀፉትን ድርጊቶች ከማድረግ እንደማይቆጠብ በበኩሉ ያስረዳል። ስለዚህም ይኸኛው በፍቅር መልክ የሚገለጸው እግዚአብሄር ምድራዊውን የአካልና የመንፈስ ደስታ ያጣመረ መሆኑን ያመለክታል። ሶስተኛው ተናጋሪ ኤሬክሲማሆስን ግን ይህ የሁለቱ አገላለጽ እስከዚህም አላረካውም። በሱም አባባል ምድራዊውና ሰማያዊው፣ መጥፎና ጥሩ ብሎ የኤሮስን ምንነት ለመግለጽ መሞከር ማለት ነገሩን አጥብቦ እንደማየት መሆኑን ያስገነዝባል። ስለዚህም ይላል፣ ኤሪክሲማሆስ፣ ኤሮስ ከዚህ አልፎ የሚሄድ በሰዎች መሀከል ያለውን ግኑኝነት ስርዓት የሚያሲዝ ብቻ ሳይሆን  የጠቅላላው የዩኒቨርስንም ህግ ያጣመረና የሚደነግግ ነው ብሎ ገለጻ ያደርጋል። ከዚህም በመነሳት በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ነገር ተነስቶ የሰዎችን የተወሳሰበ ግኑኝነት አቋርጦ በመሄድና በኮከቦችና በእግዚአብሄሮች መሀከል ያለውን ግኑኝነት በመደንገግ ማንኛውም የተፈጥሮ ህግ በመሳሳብና በመጋጨት ወይም በመራቅ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ብሎ ሰፋ ባለ መልክ ያስረዳል። ስለዚህም ይላል፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በቀናው እግዚአብሄር ቁጥጥር ስር ያሉ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት ዕውነተኛ ወንድማማችንት ይመሰረታል ይላል። በሌላ ወገን ግን ሀፍረተቢሱ ኤሮስ ጭንቅላቱ በሳይንስ በመጠመድ ወደ ቀናው መንገድ መምጣት አለበት ብሎ ንግግሩን ይደመድማል።

        ይህ ውይይት እንደቀጠለ፣ ቀልደኛው አርስቲፋኖስ ከስቅታው ቀስ በቀስ በመላቀቅ ከሁለቱ ተነጋሪዎች በተለየ መልክ ስለ ኤሮስ ምንነት ለማስረዳት ይሞክራል። ስለዚህም ይላል፣ እስካሁን ድረስ የሰውን ልጅ የጎደለው የማሰብ ኃይል ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ኤሮስ ልዩ ኃይልና የሰውንም ልጅ ከተናወጠው በሽታ የሚያድንና ወደ ክፍተኛው የኑሮ ደስታ የሚመራው ነው ብሎ ኤሮስ ምን እንደሆን በበኩሉ ይገልጻል። ሰዎች በአፈጣጠራቸው ልዩ እንደነበሩና አግዚአብሄሮችን ለመተንኮስ ሲቃጡ ዞይስ የተባለው እግዚኤብሄር ለሁለት እንደሰነጠቃቸውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጠፋባቸውን አካል ለመፈለግ ወዲህና ወዲያ ውር ውር ማለት እንደጀመሩ ይተነትናል። በዚህም ምክንያት፣ ዞይስ እንደገና የጠፋባቸውን አካል መልሰው እንዲያገኙ በማድረግ በወንድና በሴት መሀከል ልዩ ግኑኝነት እንዲመሰረት ያደርጋል። በመሆኑም እንደገና ከተሰነጠቀው የሰውነት አካል ጋር በጋብቻ መልክ በመገናኘት ሀቀኛውን ተፈጠሮአዊ ግኑኝነት መመስረት ሲችሉ፣ ይህም ዕውነተኛው ሰብአዊነት እንደሆነ ያመለክታል። አጋቶን የተባለው ጋባዥ ግን በዚህ አገላለጽ ባለመደሰት የራሱን ትንተና ይሰጣል።  በአጋቶን አገላለጽ እስካሁን ድረስ ኤሮስ ምን እንደሆነ ለመተንተን የተደረገው ሙከራ አዎንታዊ ጎኑን ብቻ ያመለከተ ሲሆን ዕውነተኛ ውስጣዊ ባህርይውን ለማስረዳት ወይም ለመረዳት እንዳልተቻለ ቅሬታውን ያሰማል። ስለዚህም ይላል፣ በመጀመሪያ ውስጣዊ ይዘቱን ወይም ምንነቱን መረዳት ሲገባ፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ተግባሩን ወይም ደግሞ ተጽዕኖውን ማስቀመጥ እንደሚቻል በበኩሉ ይናገራል። በዚህም መሰረት፣ ኤሮስ ከሁሉ እግዚአብሄሮች የመጨረሻው ሲሆን፣ በጣም ቆንጆውና ኃይለኛውም እንደሆነ ያመለክታል። ከዚህም አልፎ በመሄድ ታታሪና ሚዛናዊ ፍርድን የሚሰጥ እንደሆነ ወይንም አድልዎን የሚቃውም፣ አስተዋይነትና ብልህነት የተዋሃደው እንደሆነ ለተቀሩት ይተነትናል። ራሱንም የሚቆጣጠር፣ አድልዎም የማያጠቀውና ብልህነትን የተካነ ስለሆነ፣ ሳይንስን፣ ግጥምንና ፖለቲካን በማጣመር ዕውነተኛ ፍቅር በሰዎች መሀከል እንዲሰፍን የሚያደርግ ነው ይላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ በሰዎችና በእግዚአብሄሮች መሀከል ዕውነተኛ ፍቅር እንዲመሰረት ያደርጋል ይላል።

        በፕላቶን አገላለጽ ከላይ የተደረጉት ገለጻዎች በሙሎ በሶፊስታዊ ፍልስፍና የተካኑትን ደቀ-መዝሙሮች ሲያመለክት፣ በዚያን ጊዜ በህብረተሰባቸው ውስጥ የነበራቸውን ቦታና በህብረተሰብ ውስጥ ይንጸባረቅ የነበረውን አመለካከት የሚያረጋግጥ መሆኑን በበኩሉ ይናገራል። በሌላ ወገን ግን በግብዣው ላይ ተገኝተው ስለኤሮስ ያደረጉት ተናጋሪዎች በሙሉ በንግግራቸው ተሳክረውና ተዝናንተው ነበር። ሁሉም የየራሱ ንግግር አርክቶት ይዝናና ነበር። ይህንን የተመለከተው ሶክራተስ ግን በነሱ መሳከር በመገረም ስለኤሮስ ምንነት ማስረዳት ይጀምራል። የሶክራቶስ አገላለጽ ከሌሎች የሚለየው በራሱ ንግግር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ ሌሎችንም በጥያቄና በመልስ እንዲሳተፉ የጋበዘ ልዩ ዐይነት በሁለት ሰዎች መሀከል የተደረገ ንግግር(Dialog) ነው። በመሆኑም የሶክራተስ የአገላለጽ ዘዴ በራስ ገለጻና ዲያሎግ እንዲሁም በዕውቀትና ዕውቀትን በመፈለግ መሀከል የሚሸከረከር ልዩ ሳይንሳዊ ስልት ነው።

        ሶክራተስ፣ አጋቶን በኤሮስ ውስጣዊ ይዘትና ድርጊት(Essence and Effects) መሀከል ያለውን ልዩነት ያደረገውን ገለጻ ያሞግሳል። በዚህ መቆም እንደሌለበትም በማስረዳት፣ ኤሮስ ማለት ምን ማለት ነው? ብሎ በጥያቄ ያፋጥጣቸዋል። በዚህ ዐይነቱ ጥያቄ እስከአሁን ድረስ የተደረገው ገለጻ እንደገና በጥያቄ ውስጥ ይቀመጣል፤ ይናጋል። ስለፍቅር ወይም ኤሮስ ሲወራ ከአንድ ነገር ጋር መዋደድን ነው የሚያመለክተው። ስለዚህም ራስን ከአንድ ነገር ጋር ማገናኘት ወይም በዚያ ነገር መጠመድ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ሶክራተስ፣ ስለፍቅር ምንነትና ይህም ፍቅር ከአንድ ነገር ጋር የተያያዘ መሆኑ ከገለጸ በኋላ፣ ውስጣዊ ይዘቱን በሁለተኛው ክፍል ይተነተናል። በመጀመሪያ ግን፣ ሶክራተስ ልክ እንደ አጋቶንና እንደሌሎች ተናጋሪዎች በኤሮስ ምንነት ግራ እንደተጋባና ከሌላ ሰውም እንደተማረና ወደ ሌላ ድምደማ ላይ እንደደረሰ ለአድማጮቹ ያበስርላቸዋል። ዲያቶማ የምትባል አዋቂ ሴት፣ ኤሮስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዳስተማረችውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አስተሳሰቡ ግልጽ እየሆነ እንደመጣ ይነግራቸዋል። ብዙ ጊዜ ከዲያቶማ ጋር ከተገናኘ በኋላ ዕውነተኛ ፍቅር ምን እንደሆነ ይገነዘባል። ይህም ዕውነተኛ ፍቅር ዕውቀት ወይም ጥበብን መፈለግና በዚህ መጠመድ እንደሆነ ይነግራቸዋል። ስለዚህ፣ የሶክራትስ ፍቅር ዕውነተኛውን የዕውቀት ፈለግ ከመሻት ጋር በጥብቅ የተዛመተ ነው ማለት ነው። በዚህም መሰረት ሌሎች ከሱ ቀደም ብለው እንደገለጹት ኤሮስ እግዚአብሄር ሳይሆን፣ በመጥፎ ነገርና በጥሩ መሀከል የሚገኝ፣ ሰውን ከእግዚአብሄር ጋር የሚያገናኝ ነው። ስለዚህም ይላል ሶክራተስ፣ ጥሩው ነገር ቆንጆ ነው። በሁለቱ መሀከልም የሚገኝ ስለሆነ እንዲሁም ጥበብን በመፈለግና ይህንን ለመረዳት ባለመቻል መሀከል የሚዋልል ነው። ስለዚህም ኤሮስ እንዲፈላሰፍ ይገደዳል። እግዚአብሄር ፈላስፋ እይደለም ወይም መፈላስፈን አይፈልግም። ምክንያቱም ከመጀመሪያውኑ አዋቂ ስለሆነ መፈላሰፍ አያስፈልገውም። ሶክራተስ በመቀጠልም፣ ታዲያ ፈላስፋው ማን ነው?  ብሎ ጥያቄ ያቀርባል። አንድ ፈላስፋ አለማወቁን የሚያውቅ ብቻ ነው ብሎ ይደመድማል። በሌላ አነጋገር አንድ ሰው አለማወቁን ሲገነዘብ ለማወቅ ይገደዳል። ከመጀመሪያውኑ አውቃለሁ ብሎ የሚግደረደር ከሆነ ግን የዕውቀትን ወይም የጥበብን በር ይዘጋል። በግብዝነቱ ጭንቅላቱ ይጋረዳል። በዚህም መሰረት ዲያቶማ ኤሮስ ማለት ተፈቃሪው አንጂ አፍቃሪው እንዳለሆነ እንዳስተማረችው ይናገራል።

        ከዚህ ስንነሳ የሚቀጥለው ጥያቄ፣ ዕውነተኛ ፍቅር በአስተሳሰባችን ላይ ምን ዐይነት ተግባር ወይም ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለን ጥያቄ እንድናቀርብ እንገደዳለን። ባጭሩ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ፍቅር ደስተኛ ያደርጋል። አንድ ስሜት ቆንጆ ነገር ላይ ካተኮረ ጥሩ ነገር ለመስራት ዝግጁ ይሆናል። ስለዚህም ቆንጆን ነገር መያዝ ወይም የራስ ማድረግ ደስተኛ ያደርጋል። ዲያቶማ እጅግ በረቀቀ መንገድ ሶክራተስን በመጠየቅ በአንድ ነገር ላይ በፍቅር መጠመድ ማለት ቆንጆ ነገርንና ደስታን ከመፈለግ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ታስረዳዋለች። በአንድ ነገር በፍቅር መጠመድ ማለትም ሀብትን ማካበት ሳይሆን ወይም አንድን ነገር የራስ ማድረግ ሳይሆን፣ አንድ ጥሩ ነገር ሰርቶ ማለፍ መሆኑን ታስተምረዋለች። በዲያቶማ አገላለጽም ጥሩ ነገር በድርጊት የሚገለጽና ድርጊቱም ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ የሚተላለፍ ነው። በዚህም ምክንያት፣ አንድ ሰው አንድ ቆንጆ ነገር ለመስራት ከተጣጣረና ተግባራዊ ካደረገ ስራው ዘለዓለማዊና ስሙም ሲታወስ የሚኖር ነው ማለት ነው። ይህ ድርጊት መንፈሳዊና የሰዎችንም ባህርይና ተግባራቸውንም የሚቀርጽ ሲሆን፣ ለሰው ልጅ ጥሩ ስራ ለመስራት በፖለቲካ ታታሪነት፣ በግጥም ወይም በስዕልና የሰውን መንፈስ የሚያረጋጉና የማሰብ ኃይሉንም ከፍ በሚያደርጉ ሁኔታዎችና በሚጨበጡም ሆነ መንፈስን በሚያድሱ የሚገለጽ ነው። በዚህም ምክንያት ሳያቋርጥ ለሰው ልጅ ጥሩ ነገር ሰርቶ ጥሎ ለማለፍ የሚፈልግ ሰው ውስጣዊ የመንፈስ ደስታ ይሰማዋል። ስለሆነም፣ ዲያቶማ ለሶክራተስ ያስተማረችው ትምህርት ከራስ ተሻግሮ የሚሄድና ዘለዐለማዊነትን የሚያጎናጽፍ ነው። በዚህም ምክንያት ነው ከሶስት ሺህ ዐመት በኋላም የሶክራተስና የፕላቶን ፍልስፍናዎች በፍጹም ጊዜያዊነታቸውን ያላጡት። የሰው ልጅ እስካለም ድረስ ህያው ሆነው እንደሚቆዩ ጽሁፎችን ደጋግሞ ላነበበ በቀላሉ መረዳት ይችላል። ስለዚህም ኤሮስ በዕውነተኛ ዕውቀት የሚገለጽ ሲሆን ካለንበት ሁኔታ ተሻግረን በመሄድ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅና መልስ ለመስጠት እንድንችል የሚያደርግ ልዩ ስልት ነው። ሰለዚህም ወደዚያ ለመድረስ አምስት ደረጃዎችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ ዲያቶማ ለሶክራተስ ታስተምረዋለች። በመጀመሪያ ሀቀኛውን መንገድ የሚፈልግ፣ የሚፈልገውን ነገር ማወቅ አለበት። ይኸውም ቆንጆን ነገር መፈለግ ወይም ለመስራት መጣር ነው። ስለዚህም በቆንጆ አነጋገርና ገለጻ የሚመኘውን ነገር ለማስቀመጥ መሞከር አለበት። በዚህም መሰረት አንድ ሰው ቆንጆ ነገር ለመስራት ሲመኝ ባህርይው ሆነ አነጋገሩ እንዲሁም አረማመዱ ከሚመኘው ቆንጆ ጋር የተዋሃደ ነው ማለት ነው። ይህ ጉዳይ ግን በአንድ ነገር ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን የለበትም። ከዚያ አልፎ የሚሄድና ብዙ ነገሮችንም የሚያጣምር መሆን አለበት። በፖለቲካ አስተዳደር፣ በቆንጆና መንፈስን በሚያድሰው የህንጻ አሰራር፣ በስዕልና በሊትሬቸር፣ በግጥም፣ በጥሩ የአኗኗር ስልትና ተፈጥሮን በመንከባከብም ሆነ ለሌላውም በማሰብ የሚገለጽና ተግባራዊ በመሆን የሚረጋገጥ መሆን አለበት። ይህ የመጀመሪያው የዕውቀት መነሻ ወደ መንፈስ ቆንጆነት ያመራናል ማለት ነው ። ይህም ማለት በተጨባጭ ከምናየውና ቆንጆ ነው ብለን ከገመትነው ለየት በማለት ወደ ረቀቀ አስተሳሰብ እናመራለን። ቆንጆ ወይም ጥሩ ነገሮች ሊሰሩ ወይም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ሰውነታችን ውብ ስለሆነ ሳይሆን፣ መንፈሳችን ዕውነተኛውን መንገድ እንዲከተል የመንፈስ ተሀድሶ ካገኘን ብቻ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ ይህ ጉዳይ ከስነ-ምግባራ ጋር መያያዝ አለበት። የምናደርገውን የምናውቅ መሆን አለብን ማለት ነው። ስንበላና ስንጠጣ ወይም ከለላ ሰው ጋር ስንገናኝ ወይም ለሌላውም ኃላፊነት ሲሰማን ስነ-ምግባር ከአእምሮአችን ጋር ተዋህዷል ማለት ነው።ይህ ሶስተኛው የዕውቀት ደረጃ ወይም ቆንጆ ነገርን የመፈለጉ ጉዳይ ወደ ሳይንስና ወደ ትክክለኛው ዕውቀት እንድናመራ ያደርገናል ማለት ነው። ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ሳይንስና ቴክኖሎጂ አስፈላጊ መሆናቸው ግልጽ ይሆንለታል ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ዝግጁ የሆነ መፈላሰፍ ብቻ ሳይሆን ዕውነተኛውንም የመንፈስ ደስታ ይጎናጸፋል ማለት ነው። በዚህ መሰረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደዛሬው ሰውን የመጨፍጨፊያ መሳሪያዎች ሳይሆኑ የሰውን ኑሮ ለማቃለልና እንደ ወንድማማች በዚህች ዓለም ላይ ተፋቅሮ እንዲኖር የሚያደርገው ነው። የሶክራተስ ወይም የፕላቶን የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት ተፈጥሮናን ሰውን እንደፈለግን እንድንበዘብዝ የሚያደርገን ሳይሆን፣ በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ነገሮችን እያወጣን በስነ-ስርዓት እንድንጠቀምና ማቴሪያላዊውን ከመንፈሳዊ ደስታ ጋር እንድናጣምር የሚያደርገን ነው። ስግብግብነትንና ግብዝነትን አጥብቆ የሚቃወምና፣ በነዚህ የተወጠረ ድርጊቱ ሁሉ ተንኮልና ጠብ መጫር እንዲሁም ጦርነትን የሚያስነሳና በሰው ልጅ ዕልቂትም እየተደሰተ የሚኖር ሰው ሆኖ በአስተሳሰቡ ከማንኛውም ኮመን ሴንስ አስተሳሰብ የራቀ ነው ማለት ነው። ይህ መሰረታዊ አስተሳሰብ ዛሬ ተፈጥሮን ካለምንም አርቆ-አላሳቢነት ለማውደም የሚደረገውንና በዚህም በዚያም እያሳበቡ ጦርነት እየከፈቱ በሰው ልጅ ዕልቂት ላይ የሚደሰቱትንን የጥቂት ጉልበተኞችን ዓለም ጠጋ ብለን እንድንመረምር ይጋብዘናል። ምክንያቱም የሰው ልጅ ዋናው ተግባር የተወሳሰቡ ጦር መሳሪያዎችን እየሰሩ መፎከርና መተላለቅ ሳይሆን ሁሉም በየሃገሩ ጥሩ ነገር እየሰራና የመንፈስ ደስታን እየተጎናጸፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ጤናማ ግኑኝነት ለመፍጠርና ጥሩ ጥሩ ባህሎችን በመለዋወጥ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠንከር ነው።

       ይህንን ከላይ ለማሳየት የሞከርኩተን በሰፊው የተነተንኩት ካለምክንያት አይደለም። ጀግንነት፣ ግብዛዊነትና ስሜታዊነት በሚያጠቃውና ሎጂክና ፍልስፍና በትምህርት መልክ ጭንቅላትን ለመገንባት በማይሰጠብት እንደኛ ባለህብረተሰብ ውስጥ፣ ሌላው ቢቀር እንኳ ተማርን ከሚሉ ሰዎች ጋር ከፍተኛ አለመግባበት እየተፈጠረ ነው።  በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ዕውቀትንም ሆነ ትምህርትን በሚመለከት ከፍተኛ ክርክር ይካሄዳል። የምዕራቡ ዓለምም ዕድገትና የቴክኖሎጂ ምጥቀት የመጨረሻው እንዳልሆነና በነዚህ ሃገሮችም የወደፊቱን አረማመድና ህብረተሰብአዊ አወቃቀር በሚመለከት የጦፈ ክርክር ይካሄዳል። በተለይም ኢምፔሪሲዝም የሚባለው በክስተት ላይ የተመሰረተ ዕውቀት ባየለበት ዘመን ብዙ ህዝቦች የመንፈስ ደስታን አጥተው ሲሰቃዩ ይታያል። እንደ ህብረተሰብ ሳይንስ ያሉትን ትምህርቶች ለተመከለተ ደግሞ ከፍተኛ የርዕዮተ-ዓለም ትግል የሚካሄድበት መሆኑን በግልጽ የሚታወቅ ነው። ስለዚህም ስልጣንን የጨበጡና ከስልጣን ጋር በጥቅም የተያያዙ ጥቂት ፕሮፌሰሮች ህብረተሰቡ ተገዢ ሆኖ እንዲኖር የማያሰራጩት የተሳሳተ ዕወቀት ይህ ነው አይባልም። በሌላ በኩል ግን የምዕራቡ ዓለም ዕውቀት አንድ ወጥ ባለመሆኑና ብዙ ውዥንብርም ስለሚነዛ የትኛው ትክክል ነው ብሎ አንድ የተወሰነ አቋም ለመውሰድ የሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ወድቀናል። በተለይም ብዙ ትምህርታዊ ውይይት በማይካሄድበት እንደኛ ባለ ሃገር ውስጥ አንዳንድ የዕውቀት ዘርፎችን ጠጋ ብሎ መመልከት ለአስተሳሰብ አድማሳችን ጠቃሚ ነው ብዬ እገምታለሁ። መወያየትና ሃሳብ ለሃሳብ መጋጨት የአስተሳሰብ አድማሳችንን ያሰፋዋል። አንድ ህብረተሰብ በውይይትና በክርክር ብቻ ነው ዕድገት ሊጎናጸፍ የሚችለው።

         ለምሳሌ ኢኮኖሚክስን በሚመለከት የተለያዩ ፈላስፋዎች፣ ማለትም የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ ተመራማዎች፣ የክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የኬይንስን መንገድ የሚከተሉ ኢኮኖሚስቶች የካፒታሊስት ኢኮኖሚን በተለያየ መልክ ሲተረጉሙት፣ ሁሉም ግን የሚያወሩት ስለአንድ ነገር ብቻ ነው። ይኸውም ስለካፒታሊስት ኢኮኖሚክስ ውስጣዊ ይዘትና አሰራር ዘዴ ነው። ለምሳሌ የማርክስን ዳስ ካፒታል ያነበበ ሰው በጥብቅ የሚገነዘበው፣ ማርክስ ስለኮሙኒስት ህብረተሰብ ሳይሆን የሚተነትነው፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በምን ዐይነት ህግ እንደሚተዳደር ነው። ስለዚህም ማርክስ ስለ ዋጋ አሰላል መሰረት የሚያደርገው እንደነ ኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል አኮኖሚስቶች የመጨረሻውን የሰው ጉልበት(marginal cost) የዋጋ መተንተኛ መሰረት በማድረግ ሳይሆን፣ አንድ ሰራተኛ ተቀጥሮ በሚሰራበት ጊዜ የሚያፈሰውን የረቀቀ ጉልበት(abestract labour)፣ የሚሰራበትን ትርፍ ሰዓት የዋጋና የትርፍ መሰረት ሲያደርግ፣ ለጠቅላለው ዋጋ መለኪያ ለሰው ጉልበትና ለማቴሪያል የሚወጣው ቀጥተኛ ዋጋ የመተመኛ ዘዴ በማድረግ ነው። በዚህም መሰረት ከዚህ በቀጥታ ከሚታየውና እንደዋጋ ከሚተመነው ባሻገር ሰራተኛው ለትርፍ ተጨማሪ ሰዓት መስራት አለበት። ሶስቱም ነገሮች፣ ማለትም ለማቴሪያልና ለሰው ጉልበት እንዲሁም ትርፍ የስራ ሰዓት ተጣምረው የአንድን ዋጋ ዕቃ ይወስናሉ። የካፒታሊስቱንም የማደግና እየመላለሱ ኢንቬስት ማደረግ ይደነግጋሉ ማለት ነው። በዚህም መሰረት ካፒታሊዝም ታሪካዊና በልዩ ቦታና በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባለው ውስጣዊ ኃይል እያደገ የመጣ ነው።  ይህ ብቻ አይደለም። የማርክስ የዳስ ካፒታል አጻጻፍ የካፒታልስት ኢኮኖሚክስ እንዴት አድርጎ ከተራ ሸቀጣ ሸቀጥ ወደ ተወሳሰበ የአመራረት ዘዴና ይህም ከተሰበጣጠረ አመራረት ወደ ተጠቃለለ(monopoly) የአመራረት ዘዴ እንዳመራና የገበያም ዋጋ በነዚህ ሞኖፖሊስቶችና ኦሊጎሎፖሊስቶች እንደሚደነገግ ነው ያሚያመለክተው። ስለሆነም ይላል ማርክስ፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ከፍተኛ ውስጣዊ ኃይል ሲኖረው፣ ተቀጥሮ በሚሰራው ሰራተኛና ዋናው የትርፍ ዋጋ አመንጭ በሆነው በዚሁና በየጊዜው የሰውን ጉልበት በሚተካው ማሽን መሀከል መዛባት ይፈጠራል። በመሆኑም ትርፍ ሆኖ የሚገመተው የሰው ኃይል(redundant labour force) በማሽን እየተተካ ሲሄድ በዚያውም መጠን ትርፍ ምርት የማምረትና ትርፍን ከፍ የማድረጉ ኃይል እየቀነሰ ይሄዳል ይላል። በዚህም ምክንያት ትርፍ እየቀነሰ ሲሄድ የግዴታ ካፒታሊዝም ቀውስ ይደርስበታል ብሎ ስለካፒታሊዝም ውስጣዊ ቅራኔና ውስጠ-ኃይል(dynamism) ይነግረናል። በሌላ ወገን ግን በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት 1ኛ)ካፒታሊዝም ውስጣዊ ቅራኔ የለውም። ከውጭ በሚመጡ ነገሮች ካልሆነ በስተቀር በራሱ ውስጣዊ ቅራኔ ሊረበሽ የሚችል አይደለም ወይም ደግሞ ሁል ጊዜ ሚዛናዊ(equilibrium) በሆነ መልክ ነው የሚሰራው። 2ኛ)ሰራተኛው ትርፍ ምርት(surplus-value) ሳይሆን የሚያመርተው፣ ተጨማሪ ምርት የሚከሰተው አንድን ምርት ለማምረት በሚወጣው ወጪና ምርቱ ተሽጦ በሚገባው ትርፍ የአምራቹን ዕድገትና ውድድር ይወስናል ይላል። 3ኛ)በገበያ ላይ የሚሳተፉት ሁሉ ዕኩል ኢንፎርሜሽኖች አላቸው። ስለዚህም ተሰበጣጥረው የሚገኙ አምራችና ተጠቃሚ እንዲሁም አሰሪዎች ተመጣጣኝ የመደራደር ኃይል አላቸው። 4ኛ) የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ንጹህ በሆነ መልክ እዚህና እዚያ ተሰበጣጥረው በሚገኙ ግለሰብ አምራቾች የሚካሄድ ሲሆን፣ ወደ ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም አያመራም። 5ኛ) በማርክስና በማርክሲስት ኢኮኖሚስቶች አገላለጽ፣ ካፒታሊዝም እያደገ ሲሄድ አንዱ ሌላውን እየዋጠ በመምጣት በዚያው መጠንም የፊናንሰ ካፒታል የበላይነትን ቦታ ይወስዳል። በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች አገላለጽ ግን ይህ ዐይነቱ ግኑኘነት ኖርማልና የፊናንስ ካፒታልን የበላይነት የሚገልጽ አይደለም። ገንዘብም ቴክኒካዊ ባህርይ ብቻ ያለው እንጂ የበላይነቱን ለማሳየት የሚችል አይደለም። 6ኛ)በማርከስ፣ በተለይም በሮዛ ሉክሰምበርግ አተናተን በዚህ መልክ እያደገ የመጣው ካፒታሊዝም ሌሎች ሃገሮችን ሸቀጥ ማራገፊያው መድረክ ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም በካፒታሊሰት ሃገሮች የሚመረተው ምርት ሁሉም እዚያው ሊራገፍ ስለማይችል የግዴታ ሌሎች ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች ገበያቸውን ልቅ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ። በዚህም አማካይነት የካፒታሊስት የሀብት ክምችት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ የሶስተኛው ዓለም ሃገሮችን ወደ ንጹህ ተበዝባዥነት ይለውጣቸዋል ይላሉ። በሌላ ወገን ግን በማርክስ አባባል የካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮችን የምርት መሳሪያዎችና ግኑኝነት በመለወጥ ውስጠ-ኃይል ይሰጣቸዋል ይላል ። በዚህ አባባሉ ማርክስ ይሳሳታል። ምክንያቱም ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ከጀመረ ጀምሮ የሶስተኛው ዓለም ኢኮኖሚዎች ዝብርቅርቅ እየሆኑ መጡ እንጂ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በመጎናጸፋና ወደ ከፍተኛ የህብረተሰብ ዕደገት ደረጃ ለመሸጋገር አልቻሉም። በካፒታሊዝም ባልተስተካከለ መልክ መስፋፋት በነዚህ ወደ ኋላ በቀሩ ሃገሮች ልዩ ዐይነት ዕደገትን የሚቀናቀን ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። አዲስ የተፈጠረው ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት ውስጠ-ኃይል ኑሮት ኢኮኖሚውን ከማሳደግ ይልቅ የፍጆታ ተጠቃሚ በመሆን ሀብት አባካኝ ሊሆን በቃ። ወደ ኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ ስንመጣ ግን ይህ በሶስተኛው ዓለም ሃገሮችና በካፒታሊስት ሃገሮች የሚካሄደው የንግድ ልውውጥ ኖርማል የሆነ የስራ-ክፍፍል ውጤትና በዚህም አማካይነት ዕድገት ሊያመጣላቸው የሚችል ነው ይለናል። ይህም አባባል በታሪክ የተረጋገጠ አይደለም።  ይህም ማለት የማርክስንና የሮዛ ሉክስምበርግን አባባል ሙሉ በሙሉ ይቃረናል ማለት ነው። እዚህ ላይ ዋናው ቁም ነገር በምዕራቡ ዓለም አንድን ነገር ለመግልጽ አንድ ወጥ ዕውቀት እንደሌለና እያንዳንዱም ምሁር እንደዝንባሌውና የእሴት መሰረት አንድ የተወሰነ የአተናተን ዘዴ እንደሚጠቀምና ይህንንም ትክክል ነው ብሎ በቀበል ሌላውንም ለማሰመንና ሳያቋርጥም እንደሚታገል ለማመልከት ነው። ሰለሆነም ስለአንድ ነገርም ሆነ ሁኔታ የሚሰጠው ትርጉምም ሆነ ችግርን ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ እንደሰዎች የህብረተሰብ ዝንባሌ፣ የዕውቀት አቀሳሰምና እሴት መሰረት ይወሰናል ማለት ነው።

         ከዚህ ስንነሳ ዛሬ የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ከሃምሳ ዐመታት ባላይ የበላይነትን ተቀዳጅቶ አሁን በመንገዳገድ ላይ በሚገኝበት ወቅት እስካሁን ድረስ ሲያፋጥጡን የቆዩ ሰዎችና የዕውቀትን ልዩ ልዩ ፈለግ ለመረዳት የማይፈልጉ፣ ያሁኑን ቀውስና የሚካሄደውን የጦፈ ውይይት ጠጋ ብለው እንዲመረምሩ ራሳቸውን መጋበዝ አለባቸው። በተለይም ዛሬ በአሜሪካ ምድር ሜይን ስትሪትና ዎል ስትሪት እየተባለ ብዙም በርዕዮተ-ዓለም ሳይገፋበት የሚካሄደውን ውይይትና የኒዎ-ሊበራል ቲዎሪና ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ያስከተለውን መመሰቃቀል ጠጋ ብሎ መመልከት ያሰፈልጋል። ዛሬ በምዕራቡ ዓለም በተከሰተው የፊናንስ ቀውስ ምክንያትና በዓለም ማህበረሰብም ላይ ያስከተለውንና የሚያመጣውን አሉታዊ ውጤት አስመልክቶ የሚካሄደውን የጦፈ ውይይት ሳዳምጥና ፓል ቶክ ውስጥ ገብቼም ሆነ በዌብ ሳይት ላይ የሚወጡትን ጽሁፎች ስመለከትም ሆነ ውይይት ሳደርግ ሎጂክን ብቻ ያልተከተለ ሳይሆን በምንፈለገው ወይም በምንመኘውና ወደ ዚያ ለማምራት የትኛውን መንገድ መከተል እንዳለበን ችግር ውስጥ እንደገባንና ቢያንስ ሁለት መቶና ሶስት መቶ ዐመት እንደተጎተትን ይታየኛል። አብዛኞዎቻችንም በዚህች ዓለም ላይ የሚካሄደው መጥፎ ነገርና የገዢዎች በደል የሚመለከተን አይመስለኝም። የብዙዎቻችንም አነጋገርም ሆነ አጻጻፍ ሎጂክንና የተወሰነ ፕሪንሲፕልን ተከትሎ የማይጓዝ ነው ብል እንደ ወንጀል ወይም እንደስድብ አይቆጠርብኝም። ዛሬ ባለን እጅግ የተሰበጣጠረ አመለካከትና ዕውቀት፣ እንዲሁም የምዕራቡ ዓለም በየሃገሮች ውስጥ መግባትና መፈትፈት ወይም ደግሞ እነሱ የሚሉትን እንደትክክል አድርጎ በመውሰድ ተሸናፊነትን ማሳየት የቱን ያህል አንድ የተረጋጋና የሰለጠነ ሃገር ለመመስረት ከፍተኛ እንቅፋት እንደጣለብን ለብዙዎቻችን በግልጽ የሚታይ ነገር አይደለም። ጥቂት የሚታያቸው ግለሰቦች ደግሞ በነገሩ ገፍተው በመሄድ ለማስተማር የተዘጋጁ አይደሉም። ከዚህ የጨለመና አደናቋሪ ሁኔታ ለመላቀቅ ከተፈለገ ደግሞ አንድ ወጥ ከሆነው አመለካከት መላቀቅና ሌላ ሰው የተለየ አስተሳሰብ ሲሰነዝር ምንድነው ብሎ ከመጠየቅ ፈንታ ወደ መፎተትና የሰውን የትግል መንፈስ ካማደከም መላቀቅ አለብን። የዕውቀትን የተሰበጣጠረ ሁኔታና የሚወራውን ውዥንብር ሲገባንና ይህንንም ለመመከትና ቀናውን መንገድ ለመከተል ዝግጁ ስንሆን ታሪካዊ አስተዋጽዎ አደረግን ማለት ነው።

        እዚህ ላይ፣ ከላይ የማርከስን አገላለጽ እንደምሳሌ የወሰድኩት ነገሩን ቀላል መስሎ ስለታየኝ ነው። እዚህ ላይ የማሳስበው አሁንም የድሮው ቅዠት አለቀቀንም ወደ ሚለው ዘመቻና ዘለፋ እንዳናመራ ከመጀመሪያውኑ ለማስጠንቀቅ እፈልጋለሁ። በሌላ ወገን ደግሞ ማንኛውም ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል የአካዴሚክ ነፃነት እንዲሰማውና ይህንንም የሚቀበል መሆን አለበት። የተለያዩ አስተሳሰቦች መንሸራሸር አለባቸው። የአስተሳሰብ ጥራት እንዲረን ከተፈለገ ደግሞ ደፍረን በብዙ ነገሮች ላይ መወያየትና መከራከር አለብን። በነገራችን ላይ የማርክስ ዳስ ካፒታል በተለያዩ መልኮች በተለያዩ ምሁሮች ሲገለጽ፣ በሌላ በኩል ግን ማርክስን በቀጥታ ሳይመረኮዙ የዛሬውን የፊናንስ ገበያ ቀውስና አመጣጥ በሚገባ ቁልጭ አድርገው የሚያስቀምጡና እንከን የማይገኝላቸውም መጽሀፎች በብዛት ታትመው ገበያ ላይ ወይም በየቤተ-መጽሀፍቱ ይገኛሉ። በተጨማሪም አሁን በተከሰተው የፊናንስ ገበያ ቀውስ የማርከስ ዳስ ካፒታል በብዛት እየታተመና እየተሸጠ ነው። አታሚዎች ከተለያዩ ሃገሮች የሚመጣውን ጥያቄ(demand) ሊያሟሉ አልቻሉም።

        ወደ ዋናው መሰረተ-ሃሳቤ ልምጣና አንድን ህብረተሰብ ለመመስረት ዕውቀት መሰረታዊ መነሻ ሲሆን፣ ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ ምን ዐይነት ዕወቀት ነው የሚያስፈልገው ብሎ ጥያቄ ማቅረብ ያሰፈልጋል። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ አንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ እንዲገነባ ከተፈለገ የተወሰነ ሳይንሳዊ ፈለግን ይዞ መጓዝ አለበት። የተዘበራረቀ ዕውቀት እንደተራ ሸቀጥ እንደመሆኑ መጠን የሰዎችን ጭንቅላት በማዘበራረቅ ማንነታቸውን እንዲስቱና ርስ በርስ እንዲበላሉ ያደርጋቸዋል። ግለሰቦችም ሆነ አንድ ህብረተሰብ ታሪክ ሰሪ መሆኑ ቀርቶ ሁሉም የራሱን ጥቅም አሳዳጅ በመሆን ወደ መበላላት ያመራል። ዛሬ በሃራችን የሰፈነው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲና አገዛዙ ከፊናንስ ካፒታልና ከሲአይኤ ጋር ተቆላልፎ የሚያካሂደው የማያስፈልግ ድርጊት የዚህ የተዘበራረቀ የዕውቀት አንደኛውና ዋናው መመሪያችን ነው። አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ የሚለውም በዚህ የሚያምንና የኢትዮጵያን ህልውና ከአሜሪካ የሚሊታሪስቲክ ርዕዮተ-ዓለም ጋር አጥብቆ በማያያዝ ነው ለመታገልና ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት የሚጣጣረው። ከዚህ በመነሳት ሌሎች በፍጹም ላንግባባቸውና ግን ደግሞ የላይ  የላዩን የምንግባባቸው የሚመስሉና የምንፈልጋቸውን ነገሮች ካለብዙም ጭንቀት በተራ ሎጂክ ለማሳየት ልሞኮር። እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦች ግልጽ ማድረግና የትግል ዓላማችን እንዲሆኑ መታገል የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው።  በእሴትና በፕሪንስፕል ደረጃ መያዝ ያለባቸው መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። 1ኛ) የሰብአዊነትና የሳይንስ ጉዳይ(Humanism)፣ 2ኛ)የህብረተሰብ ጉዳይ፣ 3ኛ) የኢኮኖሚ ግንባታ ጉዳይ፣ 4ኛ) የብሄራዊ-ነፃነት ጉዳይና 5ኛ) የመንግስት ጥያቄ ጉዳይ ናቸው። እነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች ግልጽ ሲሆኑ ለምን እንደምንታገል ማወቃችን ብቻ ሳይሆን፣ የትግሉንም ጊዜ በማሳጥርና ትግላችንንም በማቃለል ወደ ቀናው የመሰባሰብና በአንድ ዓላማ የመታገል መንፈስ በማዳበር የዕድገትና የብሄራዊ ተቀናቃኝ የሆኑ ኃይሎችን የስልጣን ዘመንም ሆነ ዕድሜ ማሳጠር እንችላለን። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ኮመን ሴንስ አስተሳሰብ ምን ማለት መሆኑን ስንረዳ ከውዥንብር ዓለም መላቀቃችን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው የክርክር ዜዴና የሚመራበትንም ፍልስፍና ወይም የርዕዮተ-ዓለም መሰረት መረዳት እንችላለን።

የሰብአዊነትና(Humanism) የሳይንስ ጉዳይ !!

        በታሪካዊ ዕድገቱ ሰብአዊነት ማለት እንዲያው ለሌላው ስው ማሰብ ብቻ አይደለም። በስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የሰብአዊነት እንቅስቃሴ የተያያዘውና ዛሬም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው የሰውን ልጅ ምንነትና በዚህች ዓለም ላይ ያለውን ቦታና ድርጊት ለመግለጽ የተደረገ ትግል ነው። የሰብአዊነትም ሆነ የሳይንስ መነሻ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ከእንስሳ የተለየና በማሰብ ኃይሉ ራሱን እንደሚለውጥና አካባቢውን ቆንጆ አድርጎ የሚገነባ ነው። በዚህም መሰረት በሰው ልጅ የማሰብ ኃይልና በህዋና በኮስሞስ መሀከል ውስጣዊ ግኑኝነት አለ። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ ማንነቱንና ታሪካዊ ሰሪነቱን ሊረዳ የሚችለው የተፈጥሮንና የኮስሞስን ህግጋት ሲረዳ ብቻ ነው። ይህን ያልተረዳ ድርጊቱ የተዘበራረቀና አካባቢን የሚረብሽ፣ ኑሮውን በአቦ-ሰጡኝ የሚመራና የሚኖር ይሆናል ማለት ነው።

        ከዚህ ስነነሳ የጥንት ፈላስፋዎች የተከተሉት የምርምር መንገድ የራሳቸውንም ሆነ የተፈጥሮን ህግጋት ለመረዳት የኮስሞስን ሚዛናዊ(Harmonious) ሁኔታ እንደመነሻና እንደ መመሪያ በማድረግ ነው። በነዚህ ፈላስፋዎችም ዕምነትና የምርምር ውጤት መሰረት፣ ፕላኔቶችም ሆነ ጠቅላለው ኮስሞስ በተዘበራረቀ ሁኔታ የሚገኙ ሳይሆን በተወሰነ ፍጥነትና ርቀት የተወሰነ ህግን ተከትለው ነው የሚጓዙት። በዚህም ምክንያት በከዋክብትም ሆነ በፕላኔቶች ዘንድ የመሳሳብና የመራራቅ ሁኔታ አለ ማለት ነው።

         ወደ ምድር ስንመጣ ግን ለሰው ልጅ መኖር የሚያስፈልጉ እንደ አየር፣ውሃና ለምለም አካባቢዎች ቢገኙም፣ ከነዚህ መሰረታዊና አመቺ ሁኔታዎች ባሻገር ለሰው ልጅ ተረጋግቶ መኖር ሌሎች ነገሮች ይጎድላሉ ማለት ነው። በዚህም መሰረት የሰው ልጅ በምድር ላይ ተዘበራርቆ የሚገኘውን ነገር መልክ ማሲያዝና ቆንጆ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በዚህም ምክንያት አስተሳሰቡ የተዘበራረቀ እንዳይሆን ልክ እንደ ኮስሞስ የተወሰኑ ሳይንሳዊ ህግጋትን መከተልና እነዚህን እያሻሻለ መሄድ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግዴታ ጭንቅላቱ በልዩ ዕውቀት መገንባት አለበት ማለት ነው። ይህንን ማድረገ የማይችል ህብረተሰብ ደግሞ ኑሮው የጨለመበትና የተዘበራረቀበት ይሆናል። በዚህች ዓለም ላይ ለምን እንደሚኖር የተገነዘበ ስለማይሆን፣ እዚህና እዚያ ውርውር በማለት የተፈጥሮን ህግጋት በመጣስ የጠቅላለውን የተፈጥሮን ሁኔታ ያዛባል ማለት ነው። በዚህም መሰረት በሰዎች መሀከል ያለው ግኑኝነት የተዘበራረቀና ተፈጥሮንንም ወደ ተራ ተበዝባዥነት የሚለውጥ ይሆናል። አንድ ህብረተሰብ ደግሞ የተፈጥሮን ህግጋት የሚጥስ ከሆነና ራሱንም ለማሻሻል በየጊዜው ጥረት ካላደረገ፣ ልክ ከብቶች አንድ ቦታ ሳሩን ግጠው ግጠው ሲጨርሱ ሌላ የሚጋጥ ሳር ለመፈለግ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚጓዙ ዐይነት በመጓዝ ህይወቱ ሁሉ የተረጋጋ ሳይሆን በሂደት ላይ ብቻ ያለ እንዲሆን ይገደዳል ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነቱ የኮስሞስን ህግ መጣስና ተፈጥሮን አናግቶ የተረጋጋ ኑሮ መመስረት ያለመቻልና አዳዲስ መሳሪያዎችን እየፈጠሩ የራስን ኑሮ ለማሻሻል ያለመቻል፣ የአንድ ህብረተሰብ ወይም ሰው ጭንቅላት አስተሳሰብ በዘልማዳዊ የኑሮ ሁኔታ የተጠመደ እንደሆነ ብቻ ነው። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ በታሪኩ ውስጥ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ራሱንና እካባቢውን እየለወጠ ቢመጣምና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ጥሬ-ሀብቶችን መልካቸውንና ዐይነታቸውን እየቀየረ መጠቀሚያ ቢያደርግም፣ አንድ ስርዓትና ባህል ወይም ርዕዮተ-ዓለም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ከሰፈኑና የህዝቡን አስተሳሰብ በዚያው ብቻ ረክቶ እንዲኖር ካስገደዱት ርቆ ማሰብና እዳዲስ መሳሪያዎችን መፍጠር የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። የስራ ትርጉምንም በጠባቡ ስለሚረዳ ወደ ተወሳሰበ የስራ ክፍፍል በማምራትና ልዩ ልዩ የፍጆታም ሆነ የምርት መሳሪያዎችን በማምረትና  ኑሮውን ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማሸጋገር አዲስና ጥበብ የተሞላበት ኑሮ ለመመስርት በፍጹም አይችልም። በዚህ ላይ ደግሞ የማሰብ ኃይሉን ሊያዳብሩ የማይችሉ ቆሻሻ አስተሳሰቦች ከውጭ ከመጡ- ዛሬ በሃገራችን በግልጽ እንደምናየወ- አስተሳሰቡ ይቀጭጫል። በራሱ ላይ ዕምነት ያጣል። የውጭ ኃይሎች መጫወቻ ይሆናል ማለት ነው።

        ከሶስት ሺህ ዓመት በፊት በግሪክ የሰብአዊነት እንቅስቃሴ ሲጀመር፣ የሰውን ልጅ አስተሳሰብ ከፍ ለማድረግና ከራሱ በሻገር ርቆ በመሄድ በመንፈሳዊ ሁኔታዎች በመጠመድ ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንዲካን ነው። በዘመነ-ሬናሳንስም በዳንቴ፣ በሊዪናርዶ ዳቪንቺ፣ ማካኤል አንጀሎና እንዲሁም በፔታትራካሰና ከዚያም በኋላ በኩዛኑስ፣ በኬፕለር፣ በላይብኒዝና በገጣሚውና በቲያትር ደራሲው ፍሪድሪሽ ሺለር የፈለቁትና የተስፋፉት ዕውቀቶች በጥንታዊ ልማድና በጦር ተጠምዶ ርስ በርሱ ሲጫረስ የኖረውን የአውሮፓ ህዝብ አስተሳሰቡን ሰብስቦ ታሪካዊ ስራ እንዲሰራ ለማደረግ የተደረግ ትልቅ የጭንቅላት ትግል ነው። የሰብአዊነትና የዕውቀት መሰረቱም ይህ ሲሆን፣ ቆንጆ ቆንጆ ቤተ መንገስቶችን መስራት፣ ካቴድራሎችን መገንባት፣ ከተማዎችን መቆርቆርና የዕደ-ጥበብና የንግድ ልውውጥን ማስፋፋት፣ እንዲሁም ቆንጆ ቆንጆ የገበያ ቦታዎችንና አዳራሾችን በመስራት የሰውን ግኑኝነት ለማጠንከር አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ፣ ጥበብና የአርክቴክቸርና ስራ ሚዛናዊው ከሆነው የኮስሞስ ዓለም ጋር እንዲዋሃድ ማድረግና የሰውም አስተሳሰብ በዚህ ተጥምዶ ድርጊቱ ሁሉ በማቴሪያላዊና በመንፈሳዊ ነገሮች እንዲጠመድ ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ ዕውነተኛ የሰብአዊ እንቅስቃሴ መሰረቶች ናቸው። እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦች ተከትሎ የማይጓዝ ህብረተሰቡን ማዘበራረቅ ብቻ ሳይሆን የውጭ ኃይሎች ተገዢ በመሆን ህይወቱ በሙሉ በጦርነት እንዲጠመድ ያደረጋል ማለት ነው።

                  ከዚህ ስንነሳ ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ካፒታሊዝም የበላይነትን እየተቀዳጀና ሌሎች ሃገሮችንም ወደ ጥሬ-ሀብት አምራችነት ብቻ እየለወጠ ሲመጣ ቀደም ብሎ በምርምር የተደረሰበትን ዕውቀት በመከለስና በአፍጢሙ በመድፋት የብዙ ህዝቦች አስተሳሰብ እንዲመረዝ አደረገ። በገዢዎችና በተገዢዎች፣ በበዝባዦችና በተበዝባዦች መሀከል ልዩነት እንዲፈጠርና ዘለዓለማዊ የመንፈስ ጦርነት ሰፍኖ አንዱ ሌላውን እየፈራ እንዲኖርና ይህም ዓለም-አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው ልዩ ልዩ አሳሳች ዕውቀት የሚመስሉ መመሪያዎች በተለይም በገዢ መደቦች ዘንድ መስፋፋት ጀመሩ። በዚህ ዓይነት በተከለሰ ዕውቀት በተለይም ሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ ሃገሮች የራሳቸውን ታሪክ እንዳይሰሩና የተደላደለ ኑሮ እንዳይኖሩ ታገዱ። ሰለጠንኩና ዓለምን እመራለሁ ለሚለው የምዕራቡ ዓለም ንጹህ ጥሬ-ሀብት አምራች ወደ መሆን ተገደዱ። የተትረፈረፈ ጥሬ-ሀብታቸውን እያወጡና እያከናወኑ ለራሳቸው ከመጠቀም ይልቅ ወደ ንጹህ ባሪያነት ተቀየሩ። ደቡብ አፍሪቃ አንድ ሺህ ሜትር ወደ ታች በመቆፈርና በመሄድ ወርቅ ለማውጣት ሀይወቱን አደጋ ውስጥ የሚጥለው ጥቁሩ ደቡብ አፍሪቃዊ የዚህ የአጭበርባሪዎችና የገዢዎች ርዕዮተ-ዓለም ሰለባ ነው። በአንጎላና በናይጄሪያ የሚካሄደው የዘይት ዘረፋና አካባቢዎችን አበላሽቶ ህዝቡን መኖሪያ ማሳጣትና ጥቂቱን ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ የዚህ እጅግ የተበላሸ ዕውቀት ውጤት ነው። በየሃገሩ የተቋቋሙትም የትምህርት ዘርፎችና የሚሰጡትም ዕውቀቶች ከዕውነተኛው የሰብአዊው ትምህርት ተነጥለው በመውጣታቸው በየሃገሮች አመጸኞችና እንዲሁም ጦር ፈልፋሊዎች ብቅ እንዲሉ በማድረግ ህብረተሰብአዊ መዋከብ እንደልማድና የአኗኗር ስልት ተደርጎ በመውሰድ ህዝቦች በቀላሉ ሊሰሩ የሚችሉትንና ሃገራቸውንም ሊገነቡ የሚችሉበት ሁኔታ እየተጋረደባቸው መጣ።

            ወደ ኢትዮጵያችንም ስንመጣ እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ተብሎ የተካሄደው ትግል በሙሉ በአንድ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ዐይን ያወጣ ዘረፋና የአስተዳደር መዛባት ያላጤነ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሰብአዊነት አስተሳሰብ መርሆች ላይ ያልተመሰረተና አስተሳሰብን የሚበታትን በመሆኑ ነው። በማርከሲዝም ስም የተደረገው ትግልና ህብረተሰብአችንን በእንድ እምርታ ለመለወጥ የተደረገው ሙከራ ሊሳካ ያልቻለው ማርኪስዝምና የከበርቴው ቲዎሪዎች እየተዘበራረቁ መቅረባቸው ብቻ ሳይሆን፣ የተማሪው እንቅስቃሴ ራሱን ከሰብአዊው እንቅስቃሴ ጋር ለማገናኘት ባለመቻሉ ነው። ራሱን ለመጠየቅ ፋታ አጥቶ ወደፊት መሽምጠጡ፣ ህብረተሰብአችን ሊወጣ የማይችለው ማጥ ውስጥ ገብቶ እዚያው በዚያው እንዲንደፋደፍ ለማድረግ በቃ። ይህ ጉዳይና ጥፋት ግን በተማሪው እንቅስቃሴ ብቻ የሚላከክ ሳይሆን በስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ ሃገርን ማስተዳደር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ባለመረዳቱና ህዝቡም እንደ አንድ ህብረተሰብ እንዲያያዝ አስፈላጊዎችን የማቴሪያልም ሆነ የመንፈስ ተሃድሶ እርምጃዎች እንደሁኔታዎች እያሻሻለ ለመወሰድ ባለመቻሉም ነው።

          ወደ ዛሬው ሁኔታ ስንመጣ እጅግ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የሃገራችንን አገዛዝ ትተን፣ በመሀከላችን ያለውን ትርምስ ስንመለከት የቱን ያህል የመንፈስ ተሀድሶ ለማግኘት ተስኖን ርስ በራሳችን ስንነታረክ እንገኛለን። አንዱ ሌላውን እየወነጀለ፣ አንዱ ከሌላው የተሻልኩ ታጋይ ነኝ ብሎ በመዝናናትና ሌላውን በመዝለፍም ሆነ በማንቋሸሽ የሚያደርገው እንቅስቃሴና ትርጉም-የለሽ ትግል በተለይም የወጣቱን ጭንቅላት እየመረዘው ነው። በዚህም ምክንያት ተቃዋሚው ነኝ የሚለው ኃይል የኢትዮጵያን አንድነት እመኛለሁ፣ ዲሞክራሲን እሻለሁ ወይም ደግሞ ለገበያ ኢኮኖሚ እታገላለሁ ቢልም እነዚህ ሁሉ ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉት ከላይ በዝርዝር እንደተቀመጠው ዕውነተኛው የሰብአዊነትን የትግል ፈለግ ይዞ የማይጓዝ በመሆኑ ነው። ይህ ዐይነቱ የመጠፋፋት የትግል ስልት ጭንቅላታችን ውስጥ ከተቀረጸ ደግሞ ከአንድ ጥፋት ወደ ሌላ እየተሸጋገርን ችግሩ እንዲደራረብ በማድረግ የህዝባችንን የስልጣኔ ጥማት እንዲራዘም እናደርጋልን ማለት ነው። ስለሆነም ታጋይ ነኝ የሚለው ኃይል ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የሚገደድበት ሁኔታ አለ። ይኸውም እስካሁን ድረስ እንደታየው አይ የመበላላቱንና የመጠፋፋቱን የትግል ስልት ይዞ በመጓዝ የሃገራችንን ጥፋት ማፋጠን ወይም ደግሞ ራሱን ከህሊናው ጋር በማስታረቅ ይህች ዓለም በውሽታሞች እንደምትገዛና እንደምትበዘበዝ ተገንዝቦ ወደ ሰብአዊው የትግል እንቅስቃሴ ማምራት። በተለይም አሁን ከተከሰተው የፊናንስ ቀውስና በየቦታው ከሚካሄደው የጥቂት ጉልበተኞች ጦርነት የዓለም ህዝብ እየተገነዘበ የመጣው ነገር አለ። ይኸውም የዓለም ህዝቦች በዚህ የውሽት አገዛዝ ስልት ተተብተበው መቆየት እንደማይችሉና ንጹህ አየርን ለመተንፈስ የወንድማማችነትን አርማ ይዘው መጓዝ እንዳለባቸው ነው። በዚህም ምክንያት ነው ዛሬ በኢንዱስትሪ አገር መሪዎች ያለቀለትን የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ለማዳን ደፍ ደፍ የሚባለውና ብዝበዛውንና ጦርነቱን በሌላ መልክ ለመቀጠል ሽር ጉድ የሚባለው። ይህንን የመሪዎች ሽር ጉድ ጠጋ ብለን በመመርመር የራሳችንን ፍርድ ለመስጠት የተዘጋጀን ስንቶቻችን እንደሆን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ጉዳይም እኛንም ቢሆን በተዘዋዋሪ ስለሚመለከትንና በተለይም ደግሞ በአለፈው አስራ ስምንት ዐመታት ወደ ሃገራችን የገባው የነፃ ገበያ ርዕዮተ-ዓለም በህብረተሰብአችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላሳደረ ለወደፊቱ ትግላችን ከድሮውና ከአሁኑ ሁኔታ የምንማረው ብዙ ቁም ነገር አለ። የድሮን ወይም የአረጀን ችግር በአረጀ ዘዴ ለመፍታት እንደማንችል ሁሉ የትግላችንን ስልት የግዴታ መለወጥ አለብን። ይህንን ስናደርግ ብቻ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራመድን ማለት ነው። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣትና ህዝቦቿ በመፈቃቀርና በሰላም እንዲሁም በብልጽግና እንዲኖሩ ከተፈለገ የሰብአዊነትን የትግል ዘዴ መፈለግና ለዚህ አስተሳሰብን ማጥራት ያስፈልጋል።

የህብረተሰብ ጉዳይ

       እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያችንም ሆነ በብዙ የአፍረቃ ሃገሮች ያለው ችግር ሃገሮቻቸውን እንደ አንድ ህብረተሰብ ለማየት አለመቻልና አንድ ሃገርም እንደ አንድ ህብረተሰብ እንዲገነባ ከተፈለገ ምን ምን እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው በፍጹም ግንዛቤ ውስጥ ማሰገባት ያለመቻል ነው። ብልጣ ብልጡ የምዕራብ ዓለም ብዙ የአፍሪቃ ሃገሮችን ወደ ተራ ጥሬ ሀብት አምራችነት ከለወጠ በኋላ አገዛዞቹ ሆን ብለው የያዙት ሙያ ራሳቸውን በልዩ ልዩ የጭቆና መሳሪያ ማጠንከርና ህዝባቸውን ወደ ባርነት መቀየር ነው። ዛሬ በየቦታው ስልጣንን የጨበጡ መሪዎች ዘመናዊ በሚባል ቢሮክራሲ የሚተዳደሩ ቢመስሉም እነዚህ ቢሮክራሲያዊ መሳሪያዎቻቸውና መሪዎች ሙሉ በሙሉ ህብረተሰቡ ተዝረክርኮ እንዲኖር የሚያደርጉና ከቁጥጥር የወጡ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ናቸው።

        የሃገራችንም ሆነ የብዙ አፍሪቃ ሃገሮች ችግር የታሪክንና የህብረተሰብን ሂደት(Historical and Social processes) ያለመረዳትና የሚከተሉት ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች በሙሉ ከማዕከለኛም ሆነ ከረዢም ጊዜ አንጻር በህዝቡ የህሊና ሁኔታና በህብረተሰቡ አወቃቀር ላይ የሚያመጣውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ውጤት ከመጀመሪያውኑ በሚገባ ለመመርመር ያለመቻል ነው።  በአብዛኛዎች የአፍሪቃ ሃገሮች ብዙ ነገሮች በዘልማድና በግብር ውጣ ሰለሚሰሩ ወደ ተግባርነት የሚለወጡት ፖሊሲዎች በሙሉ ከጠቃሚነታቸው ይልቅ ጎጂነታቸው እያየለ መጥቷል። ፖሊሲዎቹ በሙሉ የህዝቦችን የማሰብ ኃይል ከማዳበርና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የስራ ክፍፍል አዳብሮ ህብረተሰቦችን እንዲረጋጋ የሚያደርጉ ከመሆናቸው ይልቅ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነትንና የአስተዳደር ጉድለትንና በደልን በማስከተል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ኑሮ ጭልሞባቸው ግራ ተጋብተው ሲሰደዱና ሲሰቃዩ ይታያል። በዚህም ምክንያት ተፈጥሮአዊ የማሰብ ኃይል እየታፈነና የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችም ኑሮ የቀን ዳቦን ከማፘፘጥ የሚያልፍ ሊሆን አልቻለም። በዚህም ምክንያት የመንግስታትና የህዝቦች ሙያ ታሪክን ከመስራት ይልቅ ተመጽዋች መሆንና ወደ ታዛዥነት መለወጥ ሆኗል። ይህ ዐይነቱ የአኗኗር ስልት ደግሞ የተፈጥሮን ህግና መብት የሚጥስ ነው። ስለሆነም በዚህ መልክ የሚተዳደሩት የአፈሪቃ መንግስታት ወዴት እንደሚያመሩና የወደፊቱስ ዕጣቸው ምን እንደሆን በቅጡ የተረዱ አይመስልም። በአገዛዞችና በህዝቦች መሀከልም ያለው አለመተማመን በየዕለቱ እየሰፋ በመምጣቱ እራሳቸውን ከህዝብ አግለው የሚኖሩት ባለስልጣን ነን ባዮች ጠቃሚውንና ለሃገሮች ግንባታ ሊያገለግል የሚችለውን ህብት በማባከን በሃገሮች ውስጥ በጣም ደሀና በጣም ጥቂት ሀብታም በመፍጠር ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጡ አድርገዋል። የሃገራችንም ሆነ የሌሎች የአፍሪቃ መሪዎች ራሳቸውን ከማደለብ በስተቀር በትክክል የሚሰሩትን የተገነዘቡ አይመስለኝም።

        አንድ ህብረተሰብ ጥቂት ስልጣንን የጨበጡና የውጭ ኃይሎችን ቡራኬ እያገኙ የሚዝናኑበት መፈንጫ አይደለም። የተፈጥሮ ህግም ይህንን አይፈቅድም። አንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ እንዲራመድና እንዲገነባና ለሚቀጥለውም ትውልድ እንዲተላለፍ ከተፈለገ ቢያንስ ከታች የሰፈሩት እንደመሰረታዊ መመሪያዎች ሆነው በጭንቅላት ውስጥ መቋጠርና ተግባራዊ መሆን አለባቸው።

          1ኛ)ማንኛውም ህብረተሰብ ፖለቲካዊና በፖለቲካ አማካይነት ሰው መሆኑን የሚገልጽበት መሳሪያ ነው። ፖለቲካ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ሲይዝ፣ ህብረተሰቦች እንደፖለቲካ ዝንባሌያቸውና አደራጃጀትና የፖለቲካ ነፃነት ሁኔታ ማደግ ይችላሉ፤ ርስ በርስ ተጋግዘው አንድ ሃገር ይገነባሉ ወይም ህልማቸው ይጨናገፋል። ሰለዚህም ፖለቲካ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ህብረተሰብ ማንነቱን የሚገልጽበት፣ ምኞቱንና ህልሙን ተግባራዊ የሚያደርግበት ልዩ ጥበባዊ መሳሪያ ነው። ፖለቲካ አንድን ህብረተሰብ በብልህነት ለማስተዳደር መጠቀሚያ መሳሪያ የሆነውን ያህል እስከተወሰነ ደረጃ ብቻ ነው ወደ ተጨባጭ ወይም ሬያል ፖለቲካ ሊለወጥ የሚችለው። ስለዚህ ፖለቲካ ጥቂት ኃይሎች ስልጣን ከጨበጡ በኋላ አንድን ህዝብም ሆነ ህብረተሰብ እንደፈለጉ የሚጨፍሩበትም ሆነ ለጦርነት የሚጋብዙበት መሳሪያ አይደለም። በሳይንስም ሆነ በተፈጥሮ ህግ መሰረት ፖለቲካ ለጥቂት ኃይሎች ብቻ ተቆርሶ የተሰጠ፣ እነሱ ሲፈልጉ ብቻ ዲሞክራሲንና ነፃነትን የሚለግሱበት መሳሪያ አይደለም። ይህንን መቀበለና ዘለዓለሙን በጭቆና ዓለም መኖርን መምረጥ በሰዎች ዘንድ ተፍጥሮአዊ እኩልነት ሊኖር አይችልም ብሎ አምኖ እንደመቀበል ይቆጠራል። ይህ ግልጽ ከሆነ ፖለቲካ መብትንና ግዴታን የሚያጠቃልል ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ግለሰቦች ለመሪነት የመመረጥ መብት ያላቸውን ያህል በዚያው መጠንም ህብረተሰብአቸውን በስነስርዓት የማስተዳደር ግዴታ አለባቸው። ይህንን የማይቀበሉና ተግባራዊ ማድረግ የማይችሉ አገዛዞች ደግሞ ለዝንተ-ዓለም ስልጣን ላይ የመቆየት መብት የላቸውም። የፖለቲካ አስተዳደር ብልሹነት ባለበት ሃገር ውስጥ አንድ ህዝብ መብቱን ለማስከበርና ነፃነትን ተቀዳጅቶ ጠንካራ ሃገር ለመገንባት ደግሞ የግዴታ ያለ የሌለውን ኃይል የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት አለው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የገዢዎች የፖለቲካ መብት የተገደበውን ያህል፣ አንድ ህዝብ ግን ከመንግስትና ከህግ በላይ እንደመሆኑ መጠን መብቱ በተረገጠ ጊዜ መብቱን የማስከበር ግዴታ አለበት። በሌላ ወገን ደግሞ ለአንድ ህብረተሰብ ህግ አስፈላጊ የሆነውንና ማንኛውም ዜጋ ህግን የማክበር ግዴታ ቢኖርበትም፣ ማንኛውንም መብቱን የሚገፍና ዕድገቱን የሚቀናቀን ህግ እንደ ህግ ብሎ ሊቀበለው አይችልም። ስለዚህ አንድ ህዝብ ከተፈጥሮ ህግ አንፃር የፈለቁትን የህብረተሰቡን ዕድገት የሚያግዝ መብት የማክበር ኃላፊነትና ግዴታ ቢኖርበትም ህግ የበላዩ ሊሆን አይችልም። መብቱን የሚያሰጠብቅ፣ ዕድገቱን የሚያግዝና የህብረተሰብ አካል መሆኑን የሚገልጽን ህግና ህገ-መንግስት ማንኛውም ዜጋ የማክበርና ተግባራዊ ማድረግና ማስከበር መብቱም ግዴታውም ነው።

        ከዚህ ቀላልና መሰረታዊ ሁኔታ ስነነሳ የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም በአለፉት ሃምሳ ዓመታት እንደህብረተሰብ መንቀሳቀስና ሃገራቸውን መገንባት ተስኖአቸው ሲለምኑ ይታያሉ። ይህ ፓለቲካን በጭንቅላቱ ገልብጦ የመረዳት ሁኔታ በብዞዎቻችን ዘንድ እስካለ ድረስ ሃገራችን እንደ ህብረተሰብ ለመመስረትና ለመጠንከር አትችልም። እስከዛሬ ድረስም ሃገራችን የጥቂቶች መጨፈሪያ በመሆንና ፖለቲካን በአፍጢሙ በመድፋት የህዝቦች ሲኦል ሆናለች። ዛሬም አገዛዙ በደል ማድረሱ ብቻ ሳይሆን ብዙ አካባቢዎች ወደ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የአኗኗር ሁኔታዎች እየለወጡ ነው። የገዢው መደብ የሚያደርገው ግራ-ገብቶት ሃገር ሲያመሰቃቅልና የተፈጥሮንና የኮስሞስን ህግ የጣሰ አሰራር በመስራት ህዝቡን በትርምስ ዓለም ውስጥ እንዲኖር አደርጓል።

      ሁለተኛውና ከዚህ ተለይቶ የማይታየው አንድ ህብረተሰብ እንደህብረተሰብ እንዲታይና እንዲገነባ ከተፈለገ ህብረተሰቡ በስራ ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የማምረትና የንግድ ልውውጥ ማካሄድ መቻል አለበት።ለዚህ ደግሞ ሳይንስና ቴክኖለጂ የግዴታ የስራ-ክፍፍሉ ዐይነተኛ አንቀሳቃሽ ይሆናሉ ማለት ነው። አንድ ህብረተሰብ በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ካልሰለጠነና በዚህም አማካይነት የንግድ ልውውጥ ካላደረገ ህብረተሰቡ እንደ ህብረተሰብ ሊያያዝ በፍጹም አይችልም። ኑሮው ሁሉ የተበጣጠሰና ከውጭ በሚመጣ ምርት የሚመታና ወደ ድህነት የሚገፈተር ይሆናል ማለት ነው።

       እስከ ዛሬ ድረስ በዘልማድም ሆነ ከውጭ በመጣ የተሳሳተ ርዕዮተ-ዓለም በመጠመድ ህብረተሰቡ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ከመጠመድና በዚህ ተመርኩዞ ምርትን ከማምረትና ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ከማስፋፋት ይልቅ ወደ ችርቻሮ ንግድ ብቻ እንዲያመራ በማድረግ ኑሮ ሁሉ የተዝረከረከ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ምክንያት ውስጣዊ ኃይል እንዳይኖረው ሆኗል። በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመመራት ሰፋ ያለ የሀብት መሰረት እንዳይጥል ታግዷል። ሰፊው ህዝብ ነፃነቱ ተገፎ ለዓለም ገበያ ቡና አምራች፣ ዛሬ ደግሞ አበባ አምራች እንዲሆን ተገዷል። መሬቱ በውጭ ከበርቴዎች እየተነጠቀ ለሃገሩ ባይተዋር እየሆነ ነው። መኖሪያውና አካባቢው እየተናጉበትና ወደ ቅኝ-ግዛትነት እየተለወጠ ነው። በዚህም ምክንያት የመፍጠር ኃይሉ ታፍኗል። በመሆኑም ለአንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ መኖር የግዴታ ሰፋ ያለ አኮኖሚያዊ መሰረትና የንግድ እንቅስቃሴ አስፈላጊዎች ናቸው። የነዚህ መሻሻል፣ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር ራስን በማቴሪያላዊ ኃይል ማሳደግና የመንፈስ ደስታን መጎናጸፍ የአንድ ህብረተሰብ ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው።

         አንድ ህብረተሰብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች የሚካሄድበት መድረክ ብቻ አይደለም። አንድ ህብረተሰብ በጊዜና በቦታ የሚለካ እንደ መሆኑ መጠን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሊዳብሩ የሚችሉት ህብረተሰቡ በከተማዎችና በመንደሮች ሲያያዝና እነዚህ ውብ ህነው ሲገነቡና ሲደራጁ፣ የህዝቡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ ኃይል ከጊዜ ወደ ጌዜ እየተሻሻለ የመጣ እንደሆን ብቻ ነው። የስራ ክፍፍል ሊዳብር የሚችለው ከተማዎችና መንደሮች ሲገነቡ ነው። ሰው ሰብሰብ ብሎ መኖር ሲችል ነው። በዚህም አማካይነት ማንኛውንም ግልጋሎት ለህብረተሰቡ ማዳረስ የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው። የዚያን ጊዜ አንድ ህዝብ የዚያ ሃገር ህዝብ መሆኑን ይረዳል። ሃገሬ ነው ብሎ ይዋደቃል። ለሃገሩ ያለው ፍቅር የጸና ይሆናል። ሃገሩን ለቆ በመውጣት  ወደ ሌላ ሃገር ተሰዶ ከመኖር ይቆጠባል። ለእናቱና ለአባቱ እንዲሁም ለዘመዶቹና አዝማዶቹ አለኝታ ይሆናል። መሪዎቻችን እንደዚህ በሰፊው ማሰብ ባለመቻላቸው እጣችን መሰደድ ሆኗል። ህልማችንና ምኞታችንን በሃገራችን ምድር ተግባራዊ እንዳናደርግ ታገደናል። ከዚህ ስንነሳ ከዛሬው ሁኔታ ባሻገር የኢትዮጵያ ህዝቦች ህልምና ምኞች ለሺህ 㗹ዐመት ተንጠልጥሎ እንዳይቀር አመለካከታችንን መቀየር አለብን ማለት ነው። ህብረተሰባችን እንደ ህብረተሰብ እንዲገነባ ከተፈለገ ህብረተሰብአችንን ወደ ተራ ሸቀጥ ማራገፊያ መድረክ መለወጥ የለብንም። ከዚህ ርካሽ ከሆነ ዛሬ ዓለምን ከወጠረው ዓለምን የሸቀጥ ማራገፊያ መድረክ ለማድረግ ከሚደረገው ሩጫ በመላቀቅ ቆንጆ ከተማዎችን የምንገነባበትና የህዝቡ አስተሳሰብ በአዲስ መንፈስ የሚታነጽበትን ሁኔታ ማዘጋጀት አለብን። ዲያቶማ ለሶክራተስ እንዳስተማረችው፣ ካለው ሁኔታ ባሻገር ማየት አለብን። ከራሳችን ይልቅ ህብረተሰብአችንን ማስቀደም አለብን። ታሪክ ሰሪዎች እንጂ ታሪክ አጉዳፊዎች ለመሆን መቅበዝበዝ የለብንም።

        በከተማዎች ዕድገትና በህዝብ መሰባሰብ ኪነት ያብባል። ሰለዚህም አንድ ህብረተሰብ ጥበባዊ ነው። በሰዕል፣ በቆንጆ ቆንጆ ህንጻዎች የሚገለጽ ነው። አንድ ህብረተሰብ የቲአትር፣ የኦፔራና የካባሬት መድረክ ነው። የሰዎችን መንፈስ ለማደስና ተፈቃቅረው እንዲኖሩ ለማድረግ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትና ልዩ ልዩ ቀልዶች በጉራማይሌ የሚቀርቡበት መድረክ ነው ። በነዚህ አማካይነት ብቻ አንድ ህብረተሰብ ራሱን ለማግኘት መቻሉ ብቻ ሳይሆን ሳይወድ በግድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ይሆናል ማለት ነው።

       የዛሬውን የኢህአዲግን አገዛዝ የህብረተሰብ ፖሊሲ ስንመለከት ህብረተሰቡን ያዘበራረቀና የህዝቡን አስተሳሰብ የበተነና የሚበታትን ነው። አገዛዙ አንድ ህብረተሰብ በምን ዐይነት ህጎች መተዳደር እንዳለበት፣ እንደ ህብረተሰብ ለመገንባትና ለመተሳሰር ምን ምን እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ግልጽ ስላልሆኑለት ህዝቡን ያምሳል። ሀገሪቱን ፣ በተለይም የባህል ከተማ ከማድረግ ይልቅ ወደ አስረሽ ምቺው ቀይፘታል። በቲያትር ቤቶችና በሙዜይሞች ከማሽብረቅ ይልቅ ቡና ቤቶችና ሆቴል ቤቶች እንዲሁም ዲሰኮቴኮች በብዛት ተስፋፍተውና መባለጊያ ቦታ ሆነው ይገኛሉ። ሃገሪቱ ልቅ በመሆኗም በተለይም ማፊያዊ ስራዎችን የሚያደራጁ ከየሃገሩ የመጡ ዜጎች እንደልብ ሲንደላቀቁና የተወሰነውን ህብረተሰብ ሲያባልጉ ይታያል። በዚህም ምክንያት እሴታዊ ስራዎች ሳይሆኑ አየር ባየር የሚነገድባት፣ ህፃናት የሚታፈኑባት ወይም ከየሆስፒታሉ የሚሰረቁበትና ኦርጋናቸው የሚሸጥባት ማንም ሊቆጣጠራት የማትችል ከተማ ሆናለች። የአገዛዙ ተግባር ወንጀል የሚሰሩና ማፊያዊ ተግባር የሚያካሂዱ ዜጎችን ከመከታተል ይልቅ ለዲሞክራሲ የሚታገሉትን ማፈን ነው ስራዬ ብሎ የተያያዘው። በዚህም ምክንያት ከራሱ ከአገዛዙ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ የውጭ ሃገር ርዳታ ሰጪዎች ሚዳው ተለቆላቸው የሃገራችንን ባህል እያበላሹና በተለይም ወጣቱን እያባለጉት ነው። ህብረተሰብአችን አልኝታ አጥቶ ሁሉ ነገር ተዘበራርቆበታል። ስለዚህም ትግላችን እጅግ ጠመዝማዛና ብዙ ነገሮችንም ያጠቃለለ መሆን አለበት ማለት ነው።

የኢኪኖሚ ጉዳይ

           ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊነት በመጠኑም ቢሆን ላይ ባጭሩ ሰፍፘል። በኛ ታጋይ ነን በምንል ኃይሎች ዘንድ አንድ ትልቅ አለመግባባት አለ። ይህም ቢሆን የኛ ጥፋት አይደለም። በዓለም ላይ የተስፋፋው የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም የብዙዎቻችንን አስተሳሰብ የኢኮኖሚን ጉዳይ በጠባቡ እንድንመለከት አድርጎናል። ለምሳሌ ስለ ሃገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ ስንጽፍ ብዛዎቻችን ተጨባጩን የኢኮኖሚ ይዘት ጠለቅ ብለን በመመርመርና የመተዳደርበትን ህግ በማጥናት ሳይሆን፣ ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ስልት ተነስተን ነው የሃገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመተንተን የምንቃጣው። በዚህም ምክንያት የኢኮኖሚውን ችግር ለመፍታት ወደ ተሳሳተ መደምደሚያ እናመራለን። ስለሆነም በተራ የገበያና የካፒታሊስት ኢኮኖሚ መሀከል ያለውን ግልጽ ልዩነት ተንትኖ ለማቅረብ አልተቻለም። በመሆኑም እንደ አይ ኤም ኤፍና የዓለም ባንክ የመሳሰሉት የኒዎ-ሊበራል ኢንቲቱሽኖች በቀላሉ ሊያታልሉን ይችላሉ። እንደሚታወቀው፣ እነዚህ ድርጅቶች ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ብዙ ሃገሮችን በማስገደድና ወደ ገበያ በመለወጥ ብዙ ህብረተሰቦችን እያወካቡ ነው። ይህንን በሚመለከት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ትችታዊ መጽሀፎች ቢኖሩም የብዞዎቻችን አስተሳሰብ በዚህ የተጣመመ የገበያ ሎጂክ ውስጥ የሚሽከረከር ነው። ስለሆነም የሃገራችን ኢኮኖሚ የማክሮ ኢኮኖሚ ከምንለው የማረሚያ መሳሪያ ባሻገር በሌላ የተሻለና ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት አፍሪ(Social Wealth) ስልት እንዴት እንደምንገነባና ከአስተዳደሩ በተሻለ ሁኔታ የኢትዮጵያን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ምን ምን አማራጭ ፖሊሲዎችና የመገንቢያ መንገዶች አሉ ብለን ለመወያየትና ለማስተማር አልቻልንም። በ18ኛው ክፍለ ዘመን በነፃ ንግድ ዙሪያ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ምድር የተካሄደውን ትግል ጠጋ ብሎ ለተመለከተ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትንና የውስጥ ገበያን በሚመለከት በአሜሪካንና በጀርመን ፈላስፋዎችም ሆነ የኢኮኖሚ ምሁሮች የእንግሊዙን የሃገር አፍራሽ የነፃ ንግድ ፖሊሲ በመቃወም የጦፈ ትግል ተካሂዷል። በአሜሪካ እነ ኬሪና ሃሚልተን፣ በአውሮፓ ደግሞ የታሪክ ትምህርት ቤት (Historical School)በመባልና በእነ ፍሪድሪሽ ሊስት፣ በነ ማክስ ዌበርና እንዲሁም ሮሽ የተካሄዱት ትግሎች የሚያረጋግጡት በእነ አዳም ስሚዝ የኢኮኖሚ ፍልስፍና አማካይነት አንድን ሃገርና ህብረተሰብ ለመገንባትና ህብረተሰብን በተለያዩ ድሮች ለማስተሳሰር እንደማይቻል ነው።

          ከላይ የዘረዘርኩትን ለማስመር፣ ስለአንድ ሃገር የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመተንተን ስንቃጣና ኢኮኖሚውም በዚህ መልክ ተገንብቶ ህብረተሰቡን ሊጠቅም ይችላል ብለን ስንነሳ ሁለት የመተንተኛ ዘዴዎችን መጠቀም እንችላለን። እነዚህ ከታች ለመተንተን የምጠቀምባቸው ዘዴዎች ከኒዎ-ሊበራል የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በብዙ መቶ እጅ ይበልጣሉ። የመጀመሪያው የማርክሲስት የኢኮኖሚ መተንተኛ ዘዴ ሲሆን፣ ማርክስ እንደሚለው አንድን የሶስተኛውን ዓለም ሃገር የኢኮኖሚ መሰረትና ውስጣዊ ህግ ለመረዳት በመጀመሪያውኑ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጣዊ ክንዋኔ መረዳት ያሰፈልጋል እንዳለው፣ ይኸኛው ዘዴ ከሞላ ጎደል የተሻለ ስዕል ይሰጠናል። በማርክስ አባባል የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዲያሌክታዊ የኢኮኖሚ ሂደት ሲሆን፣ የፍጆታ ምርት(commodity production) ክንዋኔ ቀስ በቀስ ከፊዩዳሉ የኢኮኖሚ ስልት እየተላቀቀና የህዝቡ ግኑኝነት በገንዘብ አማካይነት እየተሳሰረ መጥቶ ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት መፍጠር የቻለ ነው። በንግድ አማካይነት የገንዘብ ሀብት እያካበተ የመጣው ነጋዴ በዕደ-ጥበብ ስራ የተሰማሩትን ሰራተኞች በሱ ቁጥጥር ስር በማዋልና የፍጆታ አመራረትንም ዘዴ እንዲያሻሻሉ በማድረግ በህብረተሰቡ ውስጥ ልዩ የፍጆታ አጠቃቀም ባህል እንዲዳብር አደረገ። የፍጆታ ምርት መዳበር፣ ቀስ በቀስም አምራቹ ከምርት መሳሪያዎች መላቀቅና የባላባት መደብ በዕዳ መተብተብና ነጋዴውም ወደ ከበርቴነት መለወጥ የህብረተሰቡን አስተሳሰብም ሆነ የአመራረት ሁኔታ ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ሊለውጠው ቻለ። የከበርቴው ራሺናሊቲ መስፋፋት ምርት ቀጥታ ለፍጆታ መሆኑ ቀርቶ ለገበያና ለትርፍ ሆኖ እንዲመረትና ጥራት እንዲያገኝ ማድረግ የግዴታ የግለሰብ ካፒታሊሰቶችን መፈጠርና መወዳደር ለካፒታሊዝም ዕድገት ከፍተኛ እምርታ ሊሰጠው ቻለ። በዚህ አማካይነት ቀስ በቀስ የስራ ክፍፍል ሲዳብርና በተለይም ደግሞ ኢንዱስትሪዎች በከተማዎች ውስጥ ሲቋቋሙ ገበሬውና ዕደ-ጥበበኛው ከገጠር ወደ ከተማዎች በመሰደድ በገንዘብ እየተቀጠረ እንዲሰራ ወይም ደግሞ ወደ ሌሎች የስራ መስኮች እንዲሰማራ ተገደደ ይላል። ይህ ዐይነቱ የካፒታሊስት የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት በ18ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ላይ በተለይም በእንግሊዘ ስር እየሰደደ የመጣበት ወቅት ነበር። ይህ ሂደት ቀስ በቀስ ግልፅ የሆነ ህብረተሰብአዊ ትስስር ሲፈጥር፣ የገንዘብም ሁኔታ ከፍጆታ(Commodity) ባህርይው እየተላቀቀ በብደር ገንዘብ(Credit Money) ይተካል። የብድር ገንዘብ ወይም የወረቀት ገንዘብ መስፋፋት ከዚህ ቀደሞ የነበረውን ለካፒታሊዝም መስፋፋት ዕንቅፋት የሆነውን የወርቅ ገንዘብ በመበጣጠስ ለዕድገቱ ልዩ ዕምርታ ይሰጠዋል። በአንድ በኩል በኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለው መተሳሰር፣ በሌላ ወገን ደግሞ በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለው ግንኝነት በብድር ገንዘብ አማካይነት እየተሳሰረና እየተጠናከረ ሲሄድ፣ ካፒታሊዝም ከተራ ሸቀጣ ሸቀጥ አምራችነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር ልዩ ህብረተሰብአዊ የሀብት ክምችት(Social Capital Accumulation) እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። አሁን ካፒታሊዝም ልቅ መሆኑ ቀርቶ በዕቅድ የሚሰራና በቴክኖሎጂዎች መሻሻል ጥልቀት እያገኘ ሲመጣ በእርግጥም ወደ ውስጥ ገበያው እየተስፋፋና የሰፊውም ህዝብ የመግዛት ኃይል እያደገ ይመጣል። በተለይም የሰፊውን ህዝብ የመግዛት ኃይል ለማሳደግ ከውስጥ የአሰራር ስልት ሲቀየር፣ ወደ ውጭ ደግሞ ከገቢ ባሻገር የባንክ ብደር ከምርት ሌላ ለፍጆታም አጋዥ መሆን ቻለ። ለማሳጠር ያህል የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ከታች ወደ ላይ እያደገ የመጣና በልዩ የሀብት ክምችት ዘዴ በመጠናከር የህብረተሰቡን ግኑኝነት እየለወጠ የመጣ ነው። ስለዚህም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ኬይንስ እንዳለው በገንዘብ አማካይነት ዛሬና ነገ የሚገናኙበት፣ አስመጪና ላኪዎች የሚተሳሰሩበት፣ ብድር ዋናው የካፒታሊዝም አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነበት ሁኔታ ነው። በተጨማሪም ውድድር የጦፈበትና ምርት በጥራት የሚመረትበት፣ ከፍጀታ አልፎ ጠቅላላውን የቴክኖሎጂ መሻሻል እንዲዳብርና እንዲሻሻል ያደረገ ነው። ስለሆነም ካፒታሊዝም ሁለንታዊ እንጂ በተወሰኑ ነገሮች ላይ ያተኮረ የንግድ እንቅስቃሴ ብቻ የሚካሄድበት ስልተ-ምርት አይደለም። በዚህም መሰረት ካፒታሊዝም በአንድ የሀብት ክምችት ዘዴ(accumulation model) ሊጠቃለል የሚችል ነው። ይኸውም የፍጆታን ዕቃ በሚያመርቱ ፋብሪካዎችና የምርት መሳሪያዎችን በሚያመርቱ መሳሪያዎች መሀከል ያለው የተሳሰረ ግኑኝነት በእርግጥም ለካፒታሊስት የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ነው። የፍጆታ ዕቃ ለማምረት የሚፈልጉ ከበርቴዎች የማምረቻ መሳሪያዎችን ከሚያመርተው ክፍል ይገዛሉ። ሁለቱም መስኮች ጥሬ ሀብትም ሆነ የሰው ጉልበትና ዕውቀት ያሰፈልጋቸዋል። በምርት መሳሪያዎች ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች በሚያገኙት ገቢ በፍጆታ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የሚመረቱትን ምግብም ሆነ ሌሎች ጊዜያዊና የረዢም ዕድሜ ያላቸውን ምርቶቸ በመግዛት ይጠቀማሉ። ከሚያገኙት ገቢ የተወሰነው የፍጆታን ዕቃ ለሚያመርተው ይተላለፋል። በዚህ አማካይነትና ከባንኮች ጋር በሚፈጠረው ትስስር ዕውነተኛ ካፒታሊስታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ይፈጠራል ማለት ነው። ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትም በምናወራበት ጊዜ ከዚህ የአተናተንና የአስራር ስልት(methodology) መነሳት አለብን ማለት ነው።

          ወደ ሁለተኛው የአተናተን ወይም የማጥኛ ዘዴ ስንመጣ ደግሞ እነ ፍሪድሪሽ ሊስት የተጠቀሙበት ዘዴ እንደ ማርክሰ የማቴሪያሊስት አተናተን ስልትን በመጠቀም ሳይሆን ለአንድ ህብረተሰብም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት የሰው የማሰብ ኃይል መዳበር አለበት ከሚለው በመነሳት ነው። ለዚህ ደግሞ የግዴታ የመንግስት ሚና ከፍተኛ ቦታን ሲይዝ መንግስት በልዩ ልዩ ፖሊሲዎች አማካይነት የውስጥ ገበያ እንዲዳብር የመገናኛ ዘዴዎችን ማስፋፋት አለበት፣ ንቁ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን የብድርም ሆነ ልዩ ልዩ ድጋፎች በማግኘት ግለሰብአዊም ሆነ ህብረተሰብአዊ አስተዋፅዎ ማድረግ አለባቸው የሚል ነው። እነ ፍሪድሪሽ ሊሰት መሰረት አድርገው የተነሱት የእነ ፕላቶንን የፍልስፍና መመሪያ በማድረግ ሲሆን፣ አንድ ህብረተሰብ ሊያድግ የማይችለው የህብረተሰቡ የማሰብ ኃይል የተዘበራረቅ እንደሆን፣ የሚሰራውን በደንብ የማያውቅ ከሆነና የማሰብ ኃይሉም ለዕድገት እንቅፋት በሆኑ ነገሮች ከተጠመደ መሻሻልን አያሳይም ይላል። ስለዚህም በፊዚካል ኢኮኖሚክስ ፕርንሲፕል የማሰብ ኃይሉን በማዳበር በልዩ ልዩ ሙያዎች በመሰማራትና የተደበቀውን የመፍጠር ኃይል ከታፈነበት በማላቀቅ ራሱን አድሶ ህብረተሰብአዊ ለውጥን ማምጣት አለበት ይላል። ለዚህም ትክክለኛ ዕውቀት ዋናው መሰረት ሲሆን፣ አንድን ሃገር ለማሳደግ ከተፈለገ ለዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በሙሉ አንድ ላይ መካሄድ አለባቸው። በሌላ አነጋገር በፍሪድሪሽ እምነት አማካይነት ለአንድ ህብረተሰብ ለውጥ ዋናው መሰረት እነ አዳም ስሚዝና ሪካርዶ እንደሚሉት ንግድ ሳይሆን፣ የሰው የማሰብ ኃይል መዳበርና በዚያውም በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ማድረግና ጠቅላላውም ህዝብ የዕድገት ተካፋይ እንዲሆን ማድረግ ነው። በፍሪድሪሽ ሊስትና በተከታዮቹ ዕምነት ግለሰብአዊ ነፃነት አስፈላጊ ቢሆንም፣ በረቀቀ እጅ(Inivisible Hand) አማካይነት ዕድገት ከላይ ወደ ታች(Trickle down effect) ሊመጣ አይችልም። ግለሰብአዊ ድርጊትና አስተዋፅዎ ግን እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ያመለክታል። በመሆኑም እነ ፍሪድሪሽ ሊስት እንደዛሬው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የምጣኔን ሀብት እንደ መንደርደሪያና ወይም ዕቅድ ማውጫ ዘዴ በመውሰድና የተመጠኑ ሀብቶችንም(Scarce Resourcess) በማገጣጠም ሳይሆን፣ ከላይ እንደተቀመጠው በማሰብ ኃይል አዲስ ህብረተሰብአዊ ሀብት ማፍራት ይቻላል ከሚለው አስተሳሰብ በመነሳት ነው። በመሆኑም በፍሪድሪሽ ሊስትም ሆነ በሌሎች ከሱ ከቀደሙ ፈላስፎችና የመርካንታሊሰቶች ዕምነት ኢኮኖሚ ማለት ሌላ ትርጉም ያለው ነው። ሁለንታዊና አንድን ህብረተሰብ መገንቢያ፣ የጥሬ ሀብትን በስነ-ስርዓት መጠቀሚያ ህብረተሰብአዊ የሀብት ማከማቺያ መንገድ ነው።

          ከዚህ ስንነሳ ኢኮኖሚክስ ማለት በመጀመሪያውኑ የምጣኔ ሀብት አጠቃቀም ትምህርት አይደለም። ኢኮኖሚክስ ማለት አንድን ነገር ወይም የጥሬ ሀብት በሰው ጉልበትና የማሰብ ኃይል እንዲሁም በኃይል(Energy) አማካይነት ወደ ሌላ ነገር መለወጥ ማለት ነው። ኢኮኖሚ የምርትን እንቅስቃሴ ሲያመለክት፣ ምርት ደግሞ ጥራት የሚኖረው በሳይንስና በቴክኖሎጂ እየተደገፈ ሲመረት ብቻ ነው። ስለዚህም ምርትና ሳይንስ እንዲሁም ቴክኖሎጂ ከሰው ዕውቀት ጋር ተያይዘው የሚሄዱ እንጂ፣ ኢኮኖሚ በምጣኔ ሀብትነት ብቻ ታይቶ ከዚህ የሚታቀድና ወደ ተራ ሸቀጣ ሸቀጥነት ማምረቻነት ሊለወጥ የሚችል ትምህርታዊ መሳሪያ አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ የተፈጥሮ ሀብቶች በአንድ ቦታ ተስተካክለውና እንደልብ የሚገኙ እንዳልሆነ ይታወቃል። የአንዳንድ የተፈጥሮ ሀብቶች ተሟልቶ ወይም በበቂው አለመገኘት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ለዕድገት እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በአንድ አካባቢ ያለን ሀብት በስነስርዓት ለመጠቀም ያለመቻል ወደ ተሳሳተ የዕድገት አቅጣጫ እንድናመራ ያደርገናል። በተጨማሪም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለ የምጣኔ ሀብት በተወሰኑ ሰዎች ቁጥጥር ስር ከዋለና በሆነው ባልሆነው ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ወደ ውስጥ ህብረተሰብአዊ የሀብት ክምችት ለመፍጠር አይቻልም። ለምሳሌ መሬት በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር ከዋለ፣ ወይም በወለድ ከፍ ማለት ርካሽ ብድር ማግኘት የማይቻል ከሆነ እነዚህ ነገሮች ለዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው። እነዚህን ነገሮች ግን በፖለቲካ ስልት ማሰወገድ ይቻላል። ስለዚህም የምጣኔ-ሀብት የሚለው በሳይንስና በፖለቲካ መሳሪያዎች እንዲሁም በጠቅላላው ህዝብ የማሰብ ኃይል መዳበርና መጥኖ መጠቀም ሊወስን የሚችል ነው።

           ይህ ግልጽ ከሆነ በኢኮኖሚ አማካይነት አንድ ህብረተሰብ ራሱን የሚያወቅበት፣ ሀብት አፍርቶ ከድህነት የሚላቀቅበትና በገንዘብ አማካይነት ልውውጥ የሚደረግበት ነው። የገንዘብ ማደግና መስፋፋት እንዲሁም ልዩ ልዩ ባህርይዎች መያዝ ከጠቅላላው የኢኮኖሚ ዕድገት ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለዚህም ስለ ኢኮኖሚና ስለ ሃገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ በኒዎ-ሊበራል ስልት ህብረተሰብአችንን መለወጥ አለመቻል ብቻ ሳይሆን አቅጣጫውንም እናሳስታለን። በሌላ አነጋገር፣ በኒዎ-ሊበራል የገበያ ፍልስፍናና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሳደግ አይቻልም። ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚለውም ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ዛሬ በምዕራቡ ዓለም እንደታየው በየትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚሰጠው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሀብትን ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ሀብታሙ ወይንም እነ ኦባማ ኦውነር ሺፕ ህብረተሰብ (ownership society)እንደሚሉት ማሸጋሸጊያ መሳሪያ ዘዴ እንጂ ሀብትን በእኩልነት ማከፋፋያ መሳሪያ ወይም ደግሞ በሳይንስ አማካይነት ማዳበሪያ መንገድ አይደለም። ይህ ቢሆን ኖሩ አንድ ሰው ስምንት ሰዓት ብቻ ሰርቶ ኑሮውን ማካሄድ በቻለ ነበር። ይህም የሀብት ሽግሽግ  በመኖሩ ነው( ለምሳሌ አንድ የጀርመን ማኔጀር በዓመት 60 ሚሊዮን ኦይሮ ያገኛል፣ የጀርመን ባንክ አስተዳዳሪ 13 ሚሊዮን ኦይሮ ያገኛል ወዘተ…) በዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ሀብትን የሚያዛባና በህብረተሰብ ውስጥ ኢኮኖሚው በምን ዐይነት ህግ እንደሚተዳደር የሚገልጽ አይደለም። ለምሳሌ ስለ አሁኑ የኢኮኖሚ ቀውስም ሆነ በአጠቃላይ ለምን የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ጊዜዎችን እየጠበቀ ከፍና ዝቅ ይላል የሚል በአንድም የትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ ውስጥ ተጠቅሶ ወይም ተጽፎ አይገኝም። በሌላ በኩል ግን የማርክሲስትም ሆነ የፊዚካል ኢኮኖሚክስ ምሁሮች ይህንን በሚገባ ያሳያሉ። እነዚህ ግን ራስ ፈልጎ ካልሆነ በስተቀር መደበኛ የኢኮኖሚ ትምህርት አይደሉም።

         ወደ ሃገራችን ስንመጣ በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፍልስፍናና ፖሊሲ አማካይነት ነው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መገንባት የምንችለው ብለን ጥያቄ ከማቅረባችን በፊት ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የህብረተሰብአችንን የኢኮኖሚ ውስጣዊ ይዘትና ህግ በሚገባ መረዳት  አለብን። ከዚህ ጋር በማያያዝም ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገትና ህብረተሰብአዊ ለውጥ ነው የምንፈልገው ብለን ጥያቂ ማቅረብ አለብን። እነዚህ ሁለት መሰረተ-ሀሳቦች ግልጽ ከሆኑ ደግሞ ወደዚያ ለመድረስ እንዴት መጓዝ አለብን፣ ምን ምንስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስልቶችን መጠቀም አለብን ብለን የግዴታ ራሳችን ማስጨነቅ አለብን። ይህንን ሳናደርግ ከቀረን ለመድረስ በምንፈልገው ዓላማና በሂደት በምንከተለው ፖሊሲ ግጭቶች እየተፈጠሩ ዛሬ ሃገራችን ውስጥ እንደምናየው ወደ ማይሆንና ልንወጣ ወደ ማንችለው ሁኔታ ውስጥ ይከተናል። ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ጥያቄዎችን አንስቶ መከራከርና ወደ አንድ ሁሉንም ሊያስማማ ወደ ሚችል መደምደሚያ መድረስ መጣር ደግሞ ጤናማ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የማንኛውም ዜጋ ግዴታና ኃላፊነት ነው። እንደሚታወቀው የዛሬው ሰለጠነ የሚባለው የምዕራቡ ዓለም የጭንቅላት ስራ ውጤት ነው። የተለያየ አመለካከት ያላቸው የታገሉበት መድረክ ሲሆን የአንዱ ሃሳብ እያሸነፈና የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣ ሲሆን፣ የተሸነፈው ደግሞ ሳይተኛ ሌላ ዘዴ በመፈለግና በማንሰራራት የራሱን ህብረተሰብ ርዕይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገልበት መድረክ ነው። ለዚህም ነው ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን እስከ አስረሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የመርካንታሊዝም ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲያይል፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ የሊበራል ወይም የነፃ ንግድ ፍልስፋና ያየለውና እንደገና ደግሞ እነ ጀርመንና አሜሪካን በመርካንታሊዝም መመሪያ በመመራት ኢኮኖሚያቸውን ሊያሳድጉ የቻሉት። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላም የኬይንስ አስተሳሰብ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ፣ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ልቅ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ እንደዋና መመሪያ በመወሰድ ከኢንዲስትሪ ሃገሮች ተነስቶ ዓለምን ማዳረስ ቻለ። ዛሬ ደግሞ ኒዎ-ሊበራሊዝም ወደ መዳከም የደረሰበትና በልቅ የገበያ ኢኮኖሚ መስረት ወደ ፊት መጓዝ የማይቻልበትና ራሳቸው የኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ አራማጆችም የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያሰፈልጋል እያሉ የሚጮሁበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው። ስለዚህም የተለያዩ ኢኮኖሚ ፈላስፋዎችና ፖሊሲዎች ተግባራዊነት የኃይሎችም አሰላለፍ ለውጥ ውጤት እንደሆነ በመገንዘብ ላይ ነን ያለነው። ከዚህም ስንነሳ የሃገራችንን ችግር ፈቺዎች ራሳችን እንደመሆነችን መጠን  በአጠቃላይ ነገሮች ላይ ብቻ ማትኮር ሳይሆን ወደ ነጠላ ነገር በመግባትና በመዘርዘር የህብረተሰብአችን ችግር እንዴት እንደምንፈታና ህዝባችንም የሚመኘውን እንዲያገኝ በምናምንበት መታገል አለብን። እያንዳንዱ በሚያምንበት ፍልስፍና የመታገል መብት አለው። ነገር ግን ይህንን ዕምነቱን ወደ ውጭ ማውጣት አለበት ። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው አንድ ህብረተሰብ ኢኮኖሚውን ሊገነባና ነፃ ሊወጣ የሚችለው ብሎ ማሳመን አለበት። ትግሉ አሁን በሚታየው መልክ የሚካሄድ ከሆነ „ ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ራስ ሲይዙት ያደናግር“ ዐይነት ይሆናል ማለት ነው።

የብሄራዊ-ነፃነት ጉዳይ!

            በብዙዎቻችን አመለካከት ብሄራዊ-ነፃነት ከሃገር መያያዝ ወይም መገንጠል ጋር ነው የሚያያዘው። ለምሳሌ ብዙዎቻችን የኤርትራን መገንጠል ወይም የባህር ወደብ ማጣት ጉዳይ ከብሄራዊ ነፃነት መገርሰስ ጋር እናያይዛለን። ይህ አመለካከት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ትክክል ነው። እነ ላይብኒዝም ሆነ ሌሎች ሳይንቲስቶችም ሆኑ የህብረተሰብ ሳይንስ ምሁሮች ስለብሄራዊ ነፃነትና ስለ ሃገር ሲያወሩ ከህብረ-ብሄር(Nation-State) ምስረታና ከግለ ሰቦች ነፃነትም ሆነ አንድ ሃገር በሁለመንታዊ ጎኗ ከማደግ ጋር ተለይቶ መታየት እንደሌለበት ያስተምራሉ። ስለዚህም ይላሉ፣ እንደዚህ ዐይነት የሃገር መገነጣጠል ወደ አናሳ መንግስታት ማምራት 1ኛ)መንግስታት የነቃ ፖለቲካና ፖሊሲ መውሰድ ያቃታቸው እንደሆን፣ በዚህም ምክንያት የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ጠባብ አመለካከት ያመራል ይላሉ። 2ኛ)ለአንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረ-ብሄርና ህብረተሰብ መገንባት ዋናው መስረት የማኑፋክቱር አብዮት ማካሄድ ነው ይላሉ። ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማይታይበትና መንግስታትም ጭንቅላታቸው ታውሮ በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ አንድ ህብረተሰብ ከውጭ በሚመጣ ቆሻሻ ባህል ይፈራርሳል። ህዝቡም፣ በተለይም ደግሞ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ለብሄራዊ-ነፃነቱ ያለው አመለካከት ደካማና ጠቅላላውን ህብረተሰብአዊ ሚዛን የሚያናጋ ይሆናል ማለት ነው።

          በዚህ ሳይንሳዊና ዲያሌክቲካዊ አገላለጽ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ-ነፃነት ሊገረሰስ የቻለው በውስጥ ኃይሎች አማካይነት ነው። አንድም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አወቃቀር ዕጣ ሆኖ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከአፄ ኃይለስላሴ ጀምሮ ሳይንስን መሰረት ያላደረገ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወደ ውስጥ ሽርታታና አመጸኛ የህበረተሰብ ክፍል ብቅ እንዲል አድርጓል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ለኤምባሲዎች በጋሻ እየተለካ የተሰጣቸው መሬትና መጋለቢያ ለብሄራዊ ነፃነታቸን መቦርቦርና መዳከም ራሱን የቻለ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። ይህም የሚያሳየው የአገዛዙን ንቃተ-ህሊና ብቻ ሳይሆን የቱን ያህል ህዝባችን በአገዛዙ በንቀት ይታይ እንደነበር ነው። አንድ የገዢ መደብና የምሁር ክፍል ስለሰው ልጅ የተዛባ አመለካከት ካለው እንደዚህ ዐይነቱ ሃገርን የማስቦርቦርና የኋላ ኋላም ህብረተሰቡን እንደሚበታትነው በታሪክ የተረጋገጠ ነው። በዚህም ምክንያት ህብረተሰብን አረጋግቶና አስተካክሎ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ባሌቤት የማድረጉ ጉዳይ የት እየለሌ ይሆናል ማለት ነው።

         በአጭሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያን ህዝቦችና የብሄራዊ-ነፃነታችንን ዕጣ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ለማያይዝና በዚህም አማካይነት ዕውነተኛ ነፃነታችንን እንደምናገኝ ካመነበት ሰንብቷል። በተለይም ሌላውን ትተን የአብዮቱን ታሪክ ብቻ ስንመለከት፣ ኢትዮጵያ እንደዚያ የደማቸውና ውጣቶቿ የተከሰከሱባት በአንደኛው ጎኑ በአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም በተከፈተብን በውስጥ አርበኞት የተዘጋጀ ጦርነት ነው። ኮሙኒዝም መጣ ብሎ የተደናበረው የሚሊታሪና የሲቪል ቢሮክራሲና ጸጥታ ውስጥ የተሰገሰገው ለአሜሪካን ኤምሪያሊዝም ኢንፎርሜሽን በማቀበል የኢትዮጵያን ብሄራዊ-ነፃነት እንዲከስከስና ህዝባችን ወደ ለማኝነት እንዲወድቅ አደርጓል። በዚህ የወንብድና ሙያ የተሰማራው በኋላ የአሜሪካን ፓስፖርት እየተሰጠው አሜሪካን ገብቷል። አንዳንዱ የሰራውን ኃጢአት ይቅር በለኝ ሳይል ቤተክርስቲያን ሰጋጅ ሆኗል። ከላይ እንዳልኩት ይህ የላላ የብሄራዊ ነፃነት አመለካከት አገዛዞች ከተከተሉት በጣም ደካማ ፖሊሲና ንቃተ-ህሊናን ከማያዳብር ትምህርት ተነጥሎ ሊታይ በፍጹም አይችልም። አገዛዞች ፖሊሲያቸው አርቆ አስተዋይነት የጎደለውና በማራቅና በማቅረብ ላይ የተመሰረተ ከሆነ የተወሰነውን ህብረተሰብ አሽሽቶ የመጨረሻ መጨረሻ ምስኪኑ ህዝብ ለአደጋ እንዲጋለጥ ያደረጋል። በሌላ ወገን ደግሞ በአብዮቱ ወቅት የማርክሲዝምን አርማ ይዞ የተነሳው የተወሰነው ተራማጅ ነኝ የሚለው ንኡስ ከበርቴ ኃይልን ከማሰባሰብ ይልቅ አፈንጋጭ ፖለቲካ በማካሄድና ወጣቱን ግራ በማጋባት ሳይወድ በግድ ለብሄራዊ-ነፃነታችን መዳከምና ዛሬ ላለንበት ሁኔታ የበኩሉን አስተዋጽዎ ማድረግ ችሏል። ዛሬም ቢሆን የተወሰኑ ኃይሎች በግልጽ ከመከራከርና ወጣቱን ከማስተማር ይልቅ ቂም በቀልን ዋናው የትግል መሳሪያ በማድረግና በአሉባልታ በመጠመድ ወጣቱም ሆነ ህዝባችን ለብሄራዊ-ነፃነቱ ያለው ፍቅርና ሃገርን በጋራ የመገንባቱ ሁኔታ እንዲላላ እያደረጉ ነው።

          ወደ ዛሬው ሁኔታ ስንመጣ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የትላንትናውንም ሆነ የዛሬውንም የብሄራዊ-ነፃነት ጉዳይ ከላይ በተዘረዘረው ዲያሌክቲካዊ መነፅር ሊመለከት አይችልም። በዚህም ምክንያት የዛሬውን የብሄራዊ-ነፃነታችንን መገርሰስ ቁንጽል በሆነ መልክ ብቻ ነው የሚረዳው። የኢህአዴግን አመጣጥ ታሪክ ትተን ስልጣን ከያዘ በኋላ የተከተለውን ፖሊሲ ስንመለከት ፖሊሲው ከአንግሎ-አሜሪካን ሃገሮችን የመገነጣጠልና ህብረተሰቦችን ከማዳከም ፖሊሲ ጋር በጥብቅ እንደተያያዘ አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ የሚል ኃይል ሊያምን ወይም ሊቀበል አይችልም። ሃገርን በጎሳ መነሽነሹን ትተን ናኦሚ ክላይን(Naomi Klein) The Shock Doctrine) በሚለው መጽሀፏ እንዳመለከተችው፣ ይህ አሜሪካንና እንግሊዝ የተፈለሰፈው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለብዙ አገሮች ውድቀት ምክንያት እንደሆነና አምባገነኖችንም በየቦታው እንዳጠናከረ ነው ያመለከተችው። ሰላሳ ዐመት ያህል ከአርጀንቲና እስከ ቼሌ ድረስ በተለይም የከበርቴ መደብ ብቅ እንዳይልና የካፒታሊስት ህብረተሰብ እንዳይመሰረት የተካሄደው ፖሊሲ እነዚህ ህብረተሰቦች እንዳይረጋጉ በአሜሪካንና በእንግሊዝ የተጠነሰሰ ሴራ ለመሆኑ ከዚህ መጽሀፍም ሆነ ይህ ጸሀፊ ከአስር ዐመት በላይ በተከታተለውና ባጠናው መሰረት በሚገባ ሊገነዘብ ችሏል። ስለዚህም የብሄራዊ ነፃነታችንን መከስከስ፣ የቆሻሻ ባህል መስፋፋት፣ ወጣቱ የሚንከባከበው አጥቶ ወደ አልባሌ ቦታዎች መውደቅ፣ ከዚህ ሾክ ዶክትሪን ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ይህንን ለማየት ያለመቻልና ህዝብን ለማስተማር ጥረት አለማድረግ በራሱ ብሄራዊ-ነፃነትትን እንደመቀናቀን ይቆጠራል። በፕላቶን አነጋገር ደግሞ ሶፊስታዊ የትግል ስልት ይባላል። ታጋይ መስሎ ህብረተሰቡን የሚያተረማምስና ለዝንተ-ዓለም በድህነት ዓለም ውስጥ ዘፍቆ እንዲቆይ የሚያደርግ የትግል ዘዴ ነው ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ ለብሄራዋ-ነፃነት የሚደረገው ትግል ሁለንታዊ መሆን አለበት። ተቆንጽሎ በአገር መገንጠልና በባህር ወደብ ማጣት ብቻ የሚወሰን መሆን የለበትም። አንድ ህዝብ ከውስጥ በውጭ ዜጎች የሚናቅ ከሆነና መንፈሱ እንዲዳከም ከተደረገ መሬት ተመለሰ አልተመለሰ የሚያመጣው ፍሬ ይህ ነው ሊባል አይችልም። ስለዚህም ወስጣዊ ሁኔታዎችና የውጭው ጉዳይ አንድ ላይ መያያዝና  ከውስጥ ስንጠነክርና ጠንካራ ኢኮኖሚ ስነገነባ ብቻ የዚያን ጊዜ ብሄራዊ-ነፃነታችንን ማስከበር እንችላለን ማለት ነው።

የመንግስት ጥያቄ

          እንደሌሎች ጥያቄዎች የመንግስት ጥያቄ ግልጽ አይደለም። በተለይም የኢህአዴግ ካድሬዎችም ልብ እንዲሉት ያስፈልጋል። እነዚህኝዎች የአሜሪካን ሪፓብሊካንን ጭፍን ደጋፊዎች ዐይነት የሚመስሉ ናቸው። ግራና ቀኝ ማየት የማይችሉ። ያም ሆነ ይህ መንግስት ማለት መጨፈሪያ መሳሪያ አይደለም። መጨቆኛም አይደለም። በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ መንግስት የታሪክ ሂደት ውጤት ነው። ስለዚህም በታሪክ ውስጥ ማንኛውም መንግስት ቢሆን በድሮው መልኩና ይዘቱ ያደገ የለም። እንደ የህብረተሰቦች ንቃተ-ህሊናና እንደ ኢኮኖሚው ዕድገት የመንግስት መኪና እየተሻሻለና የህብረተሰቡን ዕድገት እያገዘ እንዲመጣ ተደርጓል። በተለይም በማዕከለኛው አውሮፓ ውስጥ በጊዜው እያደገ የመጣው የከበርቴው መደብ መንግስታዊ መዋቅሩ ለዕድገቱ እንቅፋት እየሆነበት ሲመጣ ለጥገና ለውጥ ታግሏል። የመንግስት ሥልጣንም ለከበርቴው መደብ የተሸጠበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ስለሆነም በየጊዜው የመንግስቱ መኪናና የአስተዳደር ስራዎች መሻሻል አስፈላጊ ለመሆናቸው በየጊዜው ዕድገትን ከሚፈልገው ዘንድ ምክርም ሆነ ትግል ይካሄድ ነበር።

         ወደ አገራችን ስንመጣ ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ሁሉ መንግስትንና ስልጣንን ከእግዚአብሄር የተሰጣቸው ፀጋ አድርገው ነው የሚመለከቱት። በመሆኑም ኢኮኖሚውን ለማሰዳግና የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል ይልቅ ወደ መጨቆኛ መሳሪያ ይለውጡታል። ወደ ውጭ ደግሞ ጦር ቀስቃሽ መሳሪያ በማድረግ ጠላት ያፈሩበታል። ራሱን የቻለ አፋኝ የጸታ ኃይል እያቋቋሙና እያደለቡ ከህዝቡ በመራቅ ፍዳውን ያሳዩታል። በተለይም በደርግ ጊዜ የተቋቋመው የጸጥታ ኃይል ህዝብን አፋኝ በመሆን ለብዙ ወጣት መገደልና የኋላ ኋላ ራሱ የፀጥታው የተወሰነ ክፍል በሲአይኤ በመጠለፍና በጥቅም በመገዛት ሃገር አፍራሽ ሊሆን በቅቷል። ይህንን የሚክድ የለም።

       ይህ ዐይነቱ ችግር የሚፈጠረው ከላይ እንደ ተቀመጠው ንቃታ ህሊና ባልዳበረበትና መንግሰት ራሱ የጥቂቶች ንብረት ሆኖ በሚታይበት አገር ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ ከፊዩዳላዊ አመለካከት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በአፄው ዘመን „ መንግስት አይከሰስ ሰማይ አይታረስ“ የሚባል አነጋገር አለ።  ይህ ዐይነቱ አመለካከት በሰፈነበትና ስልጣን ላይ የወጣ ሁሉ፣ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ነው መብላት እያሉ የሚባልግ ከሆነ አገር የሚባል ነገር ከቶውንም አይኖርም። ስለዚህም ስለ አገር በምናወራበት ጊዜ የመንግስትን አወቃቀርና በየጊዜው መሻሻል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋራ ማገናኘት መቻል የነቃን ፖለቲካን መከተል ነው። ይህን ዐይነቱን መሻሻል የማያደርጉ መንግስታት አሁንም ሆነ ወደ ፊት ራሳቸው በፈጠሩት ችግር እየተጥመለመሉ አንድ ቀን ራሳቸው ወድቀው ህብረተሰቡንም ይዘው ይጠፋሉ።

          ማንኛውም መንግስት በተፈጥሮ ህግ መሰረት ህዝብን የመጨፍጨፍም ሆነ  ህብረተሰብን የማዘበራረቅ መብት የለውም። አንድን ሃገር አስተዳድራለሁ የሚል በፍጹም ዘለዓለማዊ ሊሆን አይችልም። ስለዚህም የዛሬው አገዛዝ አስራስምንት ዐመታት ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ ህዝብን ማሰቃየት ትልቅ የታሪክ ወንጀል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አሁን ከምዕራቡ ዓለም ፓወር ሼሪንግ የሚል ፈሊጥ በማምጣት የህዝብን ስቃይ የሚያራዝም ስልት በአፍሪቃ ውስጥ እየተስፋፋ መጥቷል። ፓርቲዎች የሚታገሉት ወይም በምርጫ የሚወዳደሩት እንዲያው ስልጣን ላይ ቁጥጥ ለማለት አይደለም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ ህብረተሰብ መሰረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው እንደመሆኑ መጠን በምርጫ ያለውን ሁኔታ መለውጥም ሆነ ታሪክን መስራት በፍጹም አይቻልም። ይህንን የምዕራቦችን ቀልድ ትተን ምን ዐይነት መንግስት መመስረት አለበት ? እንዴትስ መመስረት እንችላለን ወደ ሚለው መስረተ-ሃሳብ ላይ ማምራትና መከራከር አስፈላጊ ይመስለኛል።

         አስተሳሰቤን ለመቋጠር፣ አንድ ነገር የምንፈለግ ከሆነ ወይም ለአንድ ህብረተሰብ እንታገላለን የምንል ከሆነ ዓላማችናና የትግል ስልታንንም ሆነ ሂደቱን በተቻለ መጠን ማስቀመጥ አለብን። ግልጽነት የሌለው የትግል ስልት ይህንን ነው የምንፈልገው ብንል እንኳ ህዝብን ከማደናበር በስተቀር የምናመጣው ፍሬ የለም። ከብዙ ህዘቦች ትግል መማር አለብን። ከደቡብ አፍሪቃ እስከ ዚምባቤ ድረስ ያለው ችግርም ሆነ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጡ የሃምሳና የስድሳ ዐመት ዕድሜ ከሞላቸው የአፍሪቃ ሃገሮች የምንቀስመው በዓላማና በትግል ሂደት ወይም ስልት ዘንድ ያለመጣጣም በመታየቱ ነው። ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ብዙ ድርጅቶችም ሆነ እንቅስቃሴዎች የፍልስፍና መመሪያ ሰለማይኖራቸውና በውስጣቸው ክርክር ስለማያዳርጉ ነው። አንድ ግለሰብ የበላይነትን ሲይዝ ሃሳብን ማፈን ይጀምራል። ይህ እንደ አገዛዝ ባህል ይወሰዳል። ስልጣን ሲያዝ ስንትና ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል መሬት ላይ እንደፈሰሰ ውሃ ይሆናል። ስለዚህም ለአንድ ህዝብ ነፃ መውጣትና የስልጣኔ ባለቤት መሆን ለሰው ልጅ መኖር ኦክስጂን እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለህብረተሰብም ዕድገት ፍልስፍናና ትክክለኛ ሳይንሳዊ አመለካከት እንዲሁም ተከታታይነት ያለው ክርክር ሊታለፉ የማይገባቸው መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። በሳይንስና በፍልስፍና አማካይነት ብቻ ነው አንድ ህብረተሰብ ማንነቱን የሚገነዘበውና የታሪክ ባለቤት ሊሆን የሚችለው።

                                                                                fekadubekele@gmx.de