[gtranslate]

በህወሃት ዘመን ሲሰራበት የነበረው ብር በአዲስ ሲተካ ግንዛቤ ውስጥ ያልገቡ ነገሮች!

-አዲስ ብር ገበያ ላይ ሲውል ሊፈታ ያልቻለው የዋጋ ግሽበትና ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች-

                                                                    ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                          12.01.2021

 

በወያኔ ዘመን ሲሰራበት የነበረውን የመገበያያ ገንዘብ በአዲስ እንዲተካ ሲደረግ የተሰራ መሠረታዊ ስህተት አለ። የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ጀረጃ እየናረ መምጣት የጀመረው የህወሃት አገዛዝ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በመመከርና በግፊት ከቋሚ የገንዘብ ልውውጥ(fixed exchange rate) ከዶላር ጋር ሲወዳደር ድሮ 2.05 የኢትዮጵያ ብር በአንድ የአሜሪካን ዶላር ይቀየር የነበረውን 5 የኢትዮጵያ ብር በአንድ የአሜሪካን ዶላር መቀየር ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ነው። በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ሎጂክ መሠረት የኢትዮጵያ ብር ከፍ ብሎ የተተመነ(over valued) ስለሆነ ለውድድር አያመችም። ሰለሆነም የገንዘቡ መጠን ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ (devaluation) እንዲል ከተደረገ እንደ ቡና የመሳሰሉ ምርቶቿን በዓለም ገበያ ላይ በብዛት በመሸጥ ብዙ የውጭ ከረንሲ ታገኛለች የሚል በኢኮኖሚ ሳይንስም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ ያልተረጋገጠ ፖሊሲ ነው።

በእርግጥ የደርግ አገዛዝ ከስልጣን ላይ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ወይም ከሌሎች ጠንካራ ከሚባሉ እንደ ኦይሮና ሌሎች ከረንሲዎች ጋር ሲወዳደር ከፍ ያለ ቢያስመስለውም በዚያን ጊዜ ከነበረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር ስንነሳ በዚያ መጠን መለወጡ በተለይም ከውጭ ዕቃ በማስመጣት አገር ቤት ውስጥ ለሚሸጡም ሆነ ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያስፈልጉ በግማሽ የተፈበረኩ ዕቃዎችንም ሆነ ማሺኖችን በዶላርም ሆነ በሌላ የዓለም ገበያ መገበያያ ገንዘብ ለሚያስመጡም ሆነ ዕቃዎችን ለሚገዛው ይህን ያህልም ውድ አልነበረም። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በነበረው የብርና የዶላር ልውውጥ(Exchange Rate) አንድ ነጋዴም ሆነ አምራች ከባንክ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ከፈለገ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ለባንኩ የሚያቀርበው 2 500 000,00 የኢትዮጵያ ብር ሲሆን፣ አሁን ባለው የብርና ዶላር ልውውጥ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት የግዴታ  39 000 000,00 የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ አለበት። ይህ ዐይነቱ የብርና የዶላር ልውውጥ የግዴታ የማምረቻ ዋጋን፣ እንዲያም ሲል ተመርተው ገበያ ላይ በሚሸጡት ምርቶች ላይ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲናር ያደርጋል። በእንደዚህ ዐይነቱ የዋጋ ግሽበት የተነሳ በቀጥታ የሚጎዳው አነስተኛና ማዕከለኛ ገቢ ያላቸው ናቸው። ይህንን ዐይነቱን በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የተደነገገ ገንዘብን የመቀነስ (Devaluation)ፖሊሲ በዋጋ ግሽበትና በተጠቃሚው ላይ ሊያስከተል የሚችለውን አደጋ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ ኃላፊዎችና የገንዘብ ሚኒስተሩ በፍጹም አላጤኑም ነበር። እነሱ የተያቸውና አሜን ብለውም የተቀበሉት የኢትዮጵያ ገንዘብ በየጊዜው የሚቀንስ ከሆነ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከውን እንደቡና የመሳሰሉትን እንደ ልብ በመሸጥ  በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ታገኛለች፤ በዚያው መጠንም ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስፈልጋትን ማሺኖችና የመለዋወጫ ዕቃዎች ለመግዛት ትችላለች የሚል ነው። ይሁንና በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ታሪክም ውስጥ ሆነ በኋላ ውጤታማ የሆኑ አገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ የውጭ ከረንሲ ለማግኘትም ሆነ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሲሉ የአገሮቻቸውን ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር በየጊዜው አልቀነሱም። የካፒታሊስት አገሮችም ሆነ በኋላ ላይ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ የቻሉት እንደ ጃፓንና ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ቻይና ወደ ውስጥ ያተኮረና ከውጭ የሚገኘውን ከረንሲ ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመቹ እንደ ማሺንና ሌሎች በግማሽ የተፈበረኩ ዕቃዎች ላይ ብቻ በማዋል ነው። በሌላ አነጋገር፣ በንግድ ልውውጥ የሚያገኙትን ዶላር የቅንጦት ዕቃዎችን በማስመጣትና ገበያቸውን ለህዝቡ  በማይጠቅሙ ዕቃዎች በማጥለቅለቅ አልነበረም ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ የበቁት። ለኢኮኖሚ ዕድገታቸውም የበለጠ የተማመኑት በዶላርና በሌላ ከረንሲ ላይ ሳይሆን በአገራቸው ገንዘብና፣ የአገራቸውን ገንዘብ ከምርት ክንውን ጋር በማያይዝና፣ በመንግስት ድጋፍ አማካይነት በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት እንዲፈጠር በማድረጋቸው ነው። የተከተሉትም የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሁለ-ገብ ሲሆን፣ በአንድ በኩል በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል ግኑኝነቶች(Linkages) እንዲፈጠሩ በማድረግ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የውስጥ ገበያው በተቋማት መደገፍ ነበረበት። በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂና፣ ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅና ተቋማትን በማጠናከር ወደ ውጭ የሚልኳቸውም ዕቃዎች የእርሻ ምርቶች ሳይሆኑ ቴክኖሎጂዎችና የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ እንደ መኪናና ቴሌቪዥን፣ እንዲሁም ሌሎች የረጅም ጊዜ የፍጆታ ዕቃዎችን እንዲሆኑ ለማድረግ በቅተዋል። ተበዳሪ ሳይሆኑ ወደ አበዳሪነት፣ ጥገኛ ሳይሆኑ ከጥገኝነት ተላቀዋል።  በእኛ አገር ግን ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና ከዚህ ጋር የተያያዘው የብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ እንዲቀንስ ማድረጉ ከጥገኝነ ሊያላቅቀን በፍጹም አልቻለም። እንደምናየው ከዚህ ፖሊሲ ጋር ተያይዘው ከኢኮኖሚው ቀውስ ባሻገርም የባህልና የስነ-ልቦና ቀውሶችና፣ እንዲሁም ደግሞ የአገር ወዳድነት ስሜት እንዲወድም ለማድረግ በቅቷል ማለት ይቻላል።

ይህ ገንዘብን የመቀነስ ፖሊሲ የጠቅላላው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድ አካል ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብር በተደጋጋሚ እንዲቀንስ ተደርጓል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን ከተደረገ ወዲህ የአገራችን የንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ እንዲዛባና የዕዳ መጠኑም በቀላሉ ለመክፈል እንዳይቻል አድርጎታል። በሌላ አነጋገር፣ አገራችን በዶላር አልተትረፈረፈችም። ከዚህም በላይ ይህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምዝበራን ያመቻቸ፣ ሀብት እንዲባክን ያደረገና ጥቂቱን ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም እንዲሆን ያደረገ ነው። በዚያው መጠንም አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም እንዲለመድ በማድረግ የንግድ ሚዛኑ እንዲዛባ ለማድረግ ችሏል። ከዚህ አልፈን ስንሄድ፣ በፖሊሲው አማካይነት የአገሪቱን ገበያ ሊያሰፋ፣ ሊያዳብርና፣ እንዲሁም ለስራ ቦታ ፈላጊው በቂ የስራ መስክ ለመክፈት የሚያስችል የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ በአገሪቱ ውስጥ ሊካሄድ አልቻለም። የስራ-ክፍፍልም በመዳበርና አገር ቤት ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅሙ ለፍጆታና ለእርሻ ስራዎች የሚያገለግሉ መሳሪዎች እንዲመረቱ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር አልቻለም። ከዚህም በላይ፣ ምርታማን ከሚያሻሽሉና ፈጠራን ከሚያዳብሩ የማኑፋክተር የመዋዕለ ነዋይ ክንዋኔዎች ይልቅ መስፋፋት የጀመረው የአገልግሎት መስኩ ነው። እንደ ሆቴል ቤቶች መሰራት፣ የንግድ መስኩ መስፋፋትና እንደ ኢንተርኔት የመሳሰሉ መደብሮች መከፈትና ትላልቅ ህንጻዎች መሰራት ኢኮኖሚውን ያደገ አስመስሎታል። እነዚህ ዐይነት ህንጻዎችና ትላልቅ ሆቴል ቤቶች ደግሞ አገር ቤት ውስጥ የሚመረተውን ኃይል(Energy)፣ ውሃና ለምግብ የሚያገለግሉ እህሎችን፣ በርበሬና ቅቤ፣ እንዲሁም ሌሎች  ነገሮችን እንዲወደዱ ለማድረግ ችለዋል። ለሰፊው ህዝብ መቅረብ ይገባቸው የነበሩ መሰረታዊ ምግቦችና እንደ ውሃ የመሳሰሉት ወደ ዘመናዊ ሆቴል ቤቶች እንዲያደሉ ተደርገዋል።  በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ  አማካይነት አዲስ ዐይነት ከውጭ አገሮች በሚመጡ ዋጋቸው ውድ የሆኑ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ዕድሜ ያላቸው የፍጆታ ዕቃዎች መለመዳቸው ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ዐይነቱ የፍጆታ አጠቃቀም የተነሳና ከአምራቹ ይልቅ ተጠቃሚው እየበዛ በመምጣቱ በተለይም በአገር ቤት ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችና የእርሻ ውጤቶች ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲናር አድርጎታል። ስለሆነም እራሱን በራሱ ሊያባዛ የሚችልና በየአቅጣጫው ሊስፋፋና እርስ በርሱ ሊያያዝ የሚችል ጠንካራና ለሰፊው ህዝብ አለኝታ ሊሆን የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት አልተቻለም።

የድሮው ገንዘብ በአዲሱ እንዲተካ ሲደረግ ለዋጋ ግሽበት መናር፣ ለንግዱ ሚዛን መዛባትና ለዕዳው መቆለል ዋናው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ተብሎ ምንም ዐይነት ጥናት አልተካሄደም። እንደመሰለኝ ከሆነ የገንዘቡ መተካት ከአንድ አኳያ ብቻ ነው የታየው። ይኸውም ወያኔን በዚህ አማካይነት ለማዳከም ይቻላል ከሚለው ስሌት ብቻ በመነሳት የተደረገ ለውጥ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ምናልባት በዚህ ዐይነቱ የገንዘብ መለወጥ የዋጋ ግሽበትንም መዋጋት ይቻላል ከሚለው ስሌት በመነሳት ሊሆን ይችላል። በሞኔታሪስት ኤኮኖሚስቶች እንደነ ሚልተን ፍሪድማን በመሳሰሉት ኢኮኖሚስቶች ሃሳብ መሰረት በአንድ አገር ውስጥ የሚከሰት የዋጋ ግሽበት ሁል ጊዜ የገንዘብ ጉዳይ ነው የሚል ነው። ስለሆነም የዋጋ ግሽበትን መዋጋት የሚቻለው በሞኔታሪ ፖሊሲ አማካይነት፣ በተለይም በወለድ(Interest Rate Policy) አማካይነት ነው። የዚህ ዐይነቱ ወለድን ከፍና ዝቅ ማድረግ ደግሞ በእኛ አገር የሚሰራ አይደለም። ምክንያቱም ለመዋዕለ-ነዋይም ሆነ የፍጆታ ዕቃን ለመግዛት ሲባል ሰፊው ህዝብ ከባንክ ስለማይበደር ነው። በተጨማሪም በእነ ፍሪድማን ዕምነት ገንዘብ ያለው ተግባር አንድ ብቻ ነው፤ ይኸውም ዕቃዎችን መግዣና መሸጫ ነው። በሌላ ወገን ግን በኬይንስና የኬይንስን ሃሳብ በሚከተሉ ኢኮኖሚስቶች ዕምነት የዋጋ ግሽብትን በወለድ መሳሪያ አማካይነት መዋጋት አይቻልም። ምክንያቱም ለዋጋ ግሽበት ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶች ብዙ ስለሆኑ ነው። ለምሳሌ በጥሬ-ሀብት መወደድ የተነሳና በተለይም ኢኮኖሚው እየጋለ በሚመጣበት ጊዜ ውድድር ሲጨምርና በዚያው መጠንም ጠያቂው ሲበዛ የዕቃዎች ዋጋ ሊወደድ ይችላል። ይህ ዐይነቱ የዋጋ ጭማሪ ደግሞ ጊዜያዊና በቴክኖሎጂ መሻሻልና በኢንዱስትሪዎች ምርታማነት የተነሳ የማምረቻ ዋጋ ስለሚቀንስ የግዴታ ግሽበትም ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ ይመጣል። ያለፉትን ሰላሳ ዓመታት የአብዛኛዎችን የካፒታሊስት አገሮችን ኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ ለተከታተለ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሽከረከረው የገንዘብ መጠን እየጨመረ ቢመጣም፣ በተለይም በፍጆታ ዕቃዎች ላይ፣ ለሰፊው ህዝብ የቀን ተቀን ጠቀሜታ በሚያገለግሉት ነገሮች ላይ፣ እንደምግብና ዘይት፣ ውሃና መብራት ላይ የዋጋ ንረት በፍጹም አይታይም። የዋጋ ንረት የሚታየው በቤት ግዢና ቤት ኪራይ ላይ ነው። ይኸውም በትላልቅ ከተሞች ውስጥ ነው። ቤትን ለመግዛትም ሆነ ለመከራየት ዋናው ምክንያት ደግሞ በተለይም ከ2008 ዓ.ም የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ የካፒታሊስት አገሮች ማዕከላዊ ባንኮች ለንግድ ባንኮችና ለሌሎች አየር ባየር ለሚነግዱ የሚያበድሯቸውን ገንዝብ ወለዱን ወደ ዜሮ እንዲጠጋ አድርገውታል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ኢንቬስተሮች ለሚባሉት በርካሽ ዋጋ የሚሰጠው ብድር፣ ቤት መስሪያ፣ ያረጁ የሚመስሉ ቤቶችን ገዝቶ አድሶ መሸጥ ወይም ማከራየት እየተለመደ በመምጣቱ በተለይም የትላልቅ ቤቶች አከራዮችንና በዚህም አማካይነት የአየር በአየር ንግድ ለሚያደርጉት አመቺ ሁኔታ ስለተፈጠረ የመሬትም ሆነ የቤት መስሪያና መሸጥ፣ እንዲሁም ደግሞ ማከራየት ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ እየናረ ሊመጣ ችሏል። ይህ ዐይነቱ የማዕከላዊ ባንኮች ለንግድ ባንኮችና ስፔኩሌት ለሚያደርጉ የሚሰጧቸው ብድር ወለዱ ወደ ዜሮ እንዲጠጋ ማድረጉ ሆን ተብሎና በዚህ አማካይነት በጥቂቶች እጅ ሀብት እየተከማቸ እንዲመጣ ለማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ከባንኮች በርካሽ ወለድ ለጥቂት ሀብታሞች  የሚሰጠው ብድር የበለጠ ሀብታሞች እንዲሆኑና በተጠቃሚው ላይም ሆነ በራሳቸው መንግስታት ላይ ጫና እንዲያድርጉ አስችሏቸዋል። ከዚህ ስንነሳ፣ በኬይንስ ዕምነት ገንዘብ መግዣና መሸጫ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ስፔኩሌት ማድረጊያና ሀብትም ማከማቺያ ዘዴ ነው። በሌላ አነጋገር ቋሚ ሀብትን በመሸጥና ገንዝቡን ባንክ ውስጥ በማስቀመጥና አክሲዮን በመግዛት ገንዘብን ትርፋማ ማድረግ ይቻላል። ወደ አገራችን ስንመጣ የማዕከላዊ ባንኩም ሆነ የገንዘብ ሚኒስተሩ የተከተሉትና አሁንም የሚከተሉት ፖሊሲ የእነ ሚልተን ፍሪድማንን አስተሳሰብ በመውሰድ ነው። ይሁንና ግን እነ ፍሪድማን ያዳበሩት የሞኔተሪ ፖሊሲ በቴክኖሎጂና ሳይንስ ላይ ከሚንቀሳቀስና ከተወሳሰበ ኢኮኖሚ በመነሳት እንጂ እንደኛ አገር ካለው በአብዛኛው ከእጅ ወደ አፍ በሚመረት የምርት ክንውንና(Subsistence Economy) የፍጆታ አጠቃቀም በመነሳት አይደለም። በተጨማሪም ከተዝረከረከና፣ በአብዛኛው አገሪቱ ውስጥ በባንኮች አማካይነት ገንዘብ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ በማይተላለፍበትና የባንክም እንቅስቃሴ ባልተስፋፋበት አገር ነው።

ወደ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ ስንመጣ ማንኛውንም አንድን አገርና ህዝብ የሚመለከቱ ፖሊሲ ነክ ነገሮችም ሆኑ፣ ወይም ደግሞ ፖለቲካዎች ከመነደፋቸውም ሆነ ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት ችግሮች የሚታዩ ከሆነ ለችግሮቹ እንደ ዋና መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉት ነገሮች ከሁሉም አቅጣጫ መመርመርና መታየት አለባቸው። የበሽታው ዋና ምክንያት እስካካልተገኘ ድረስ ደግሞ አጠቃላይ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውስንም ሆነ በተለይም ደግሞ የዋጋ ግሽበትን መዋጋት በፍጹም አይቻልም። በሌላ አነጋገር፣ የድሮው ገንዘብ በአዲሱ ሲተካ የፖሊሲ ለውጥ አልተደረገም። ይህም ማለት አዲሱ የለውጥ ኃይል እየተባለ የሚወደሰው የዶ/ር አቢይ አገዛዝ አሁንም ቢሆን የሚከተለው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲን ነው። ስለሆነም ችግሩን በፈጠረው ፖሊሲ አማካይነት በግልጽ የሚታየውን የኢኮኖሚ ቀውስና፣ በተለይም ደግሞ የዋጋ ግሽበትን መዋጋት በፍጹም አይቻልም።  በሁለተኛ ደረጃ፣ አዲሱን ገንዘብ አንድ በአንድ ከመቀየር ይልቅ አንድ ብር በሶስት ወይም በአራት ቢቀየር ኖሮ ካለ አግባብ ገበያ ውስጥ የሚሽከረከረውንና በየጓዳ ውስጥ የተከማቸውን ገንዘብ ከጥቅም ውጭ ማድረግ ይቻል ነበር። ሁሉም ሰው እንዳይጎዳ ደግሞ ልውውጡን ግለሰቦች እንዳላቸው የገንዘብ መጠንና፣ በተለይም ደግሞ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያላቸው ከሆነ ይህን ያህል ገንዘብ ከየት እንዳመጡ ከተመረመረ በኋላ አዲሱን የኢትዮጵያ ብር በድሮው አንድ በአንድ ከመለወጥ ይልቅ ደረጃ በደረጃ አንድ በሁለት፣ አንድ በሶስትና በአራት መለወጥ ይቻል ነበር። ይህ  ደግሞ ቲክኒካዊ ጉዳይ ነው።  በተጨማሪም፣ የጥቁር ገበያውንም ሆነ የአየር በአየርን ንግድ ለመቆጣጠር ብርን ከዶላር ጋር ሲወዳደር ቋሚ ማድረግ ያስፈልግ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ከእንግዲህ ወዲያ ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር በአቅራቢና በጠያቂ አማካይነት እንዳይተመን ማድረግ፤ በየጊዜውም የቅነሳ ፖሊሲ አለማድረግ።  ከዚህም በላይ የጥቁር ገበያ የሚካሄድባቸውን ወይም የጥቁር ገበያ ተብለው የሚጠሩ ቦታዎችን በቁጥጥር ስር ማድረግና፣ በባንክ ከተተመነው የመለወጫ ውጭ የሚለውጡ ካሉ በህግ መቅጣት። አገር ቤት ውስጥ የሚገባውን ዶላር በሰዎች ሳይሆን በባንኮች አማካይነት ብቻ ማድረግ።  ከዚህም በላይ፣ ከአገልግሎት ኢኮኖሚ ክንዋኔ ይልቅ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሠረተ፣ ሰፋ ወዳለና ሰፊው ህዝብ ገዝቶ ሊጠቀመው የሚችል በማኑፋክተር ላይ የተመረኮዘ ልዩ ልዩ ዐይነት ምርቶችን ማምረት ያስፈልጋል። የገበያ ቁጥጥርና፣ በተለይም የዋጋን ቁጥጥር ማደረግ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም፣ ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የማይጠቅሙ ምርቶችን አለማስገባት፣ ማስመጣት የሚያስፈልግ ከሆነ ደግሞ የማስመጫ ዋጋቸውን በከፍተኛ ደራጃ እንዲጨምሩ ማድረግና፣ በመጀመሪያ ምን ምን ነገሮች ለአገር ዕድገት እንደሚያስፈልጉ ማጥናትና በአስፈላጊ ነገሮች ላይ ብቻ ማትኮር። ሁሉንም ነገር ከውጭ ማስመጣት፣ ወይም ማግበስበስና ገበያውንም ክፍት ወይም ልቅ ማድረግ አለብህ የሚል የተፈጥሮ ህግ የለም። እንደዚህ ዐይነቱ ገበያን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚም በገበያ ኃይሎች(Market Forces) አማካይነት ብቻ ነው ሊያድግ የሚችለው የሚለው አስተሳሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘ የተወሰኑ እኮኖሚስቶች ያፈለቁት ሃሳብ ነው። በዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የማይስማሙ ኢኮኖሚስቶች እንደሚያረጋግጡትና፣ የአደጉና ከኋላ በመነሳት ሁለ-ገብ የሆነ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮች ኢኮኖሚዎችን ታሪክ ስንመለከት በመጀመሪያ ደረጃ ያተኮሩት የአገራቸውን ኢኮኖሚ በማሳደግና፣ ያለውን ሀብት ለውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት በማዋል ብቻ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በፈላስፋዎችና ተቀባይነት ያገኘውን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ቲዎሪን በሚቃወሙ የተገለጸላቸው ኢኮኖሚስቶች ዕምነት ልቅ የሆነ ነጻ ገበያና ንግድ፣ እንዲሁም ግሎባላይዜሽን አማካይነት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ፣ እንዲሁም የኢኮሎጂን ቀውስ በማስከተሉና በማስፋፋቱ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ተከታታይነት ወዳለውና የተፈጥሮ-ሀብትን በተቆጠበ መልክ በሚጠቅም የኢኮኖሚ አመራረትና የፍጆታ አጠቃቀም ዘዴ መተካት አለበት እየተባለ ከፍተኛ ምሁራዊ ትግል እየተካሄደ ነው። ስለሆነም ይላሉ ይህን ዐይነቱን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራኖች፣ የሰው ልጅ ይህንንም ሆነ ያንን እየገዛ መጠቀም የለበትም። የሚያስፈልገውን ብቻ ከተጠቀመ ጤንነቱንም ሆነ የአካባቢን ሁኔታ መጠበቅና ማስጠበቅ ይቻላል ይሉናል።

ከዚህ ስንነሳ አንዳች ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊስ ሲነደፍ ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ስርዓትም እንደምንፈልግ ማወቅ አለብን። ምን ምን ነገሮችም ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ግንዛቤ እንዲኖር ያስፈልጋል።  ሰፊውን ህዝብ የማይጠቅም ኢኮኖሚና በውጭ ኃይሎች እየተገፋን ተግባራዊ የምናደርገው ሳይንሰ-አልባ የሆነና፣ በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ ያልተረጋገጠ ፖሊሲ ተግባራዊ እስከሆነ ድረስ ቸግሩ ይባባሳል እንጂ በፍጹም አይፈታም። በተጨማሪም ለችግሩ ዋና ምክንያት የሆኑት ሰዎች አሁንም በአማካሪነት የሚሰሩ እስከሆነ ደረስ የህዝባችን መሰረታዊ ፍላጎቶች አይፈቱም። በመሠረቱ የአኮኖሚ ፖሊሲ ማለት አገርን መገንቢያ መሳሪያ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አንድ አገር ዝብርቅርቋ የሚወጣና፣ አብዛኛው ህዝብም ደሀ እየሆነ መምጣት ያለበት ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሌሎች ዕውቀቶች፣ ማለትም ከፊዚክስ፣ ከባዮሎጂ፣ ከኬሚስትሪና ከሌሎች ዕውቀቶች ጋር በመቀናጀት አንድ አገር ጥበባዊ በሆነ መንገድ መገንቢያ መሳሪያ ነው።የአንድን አገር ኢኮኖሚ የማምረት ኃይል ከፍ ለማድረግ የሚያስችልና፣ በመጀመሪያ ደረጃ የህዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች መፍቺያ መሳሪያ ነው። ይህንን ማድረግ የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፖሊሲ ተብሎ ሊጠራ በፍጹም አይችልም። መልካም ግንዛቤ!!

 

 

 

                                                                                                                                                                                                                                                        fekadubekele@gmx.de