[gtranslate]

አንድን ግለሰብ ማምለክና ማመን የሚያስከትለው አደጋ!

                                      ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                         ህዳር  01 2023

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለተመለከተ፣ ፖለቲካ ካልነው አንድን ግለሰብ በማመለክ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ፖለቲካ ቲዎሪና ለፖለቲካ ነፃነት የተደረገውን ትግል ላነበበና ለተከታተለ በመሰረቱ ፖለቲካ የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት የሚሰፍንበት፣ ወይም አንድን ግለሰብ ብቻ በማምለክ ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሌለበት ልንገነዘብ እንችላለን። በመሰረቱ የፖለቲካ ፅንሰ-ሃሳብና ይዘት ዋና ዓላማ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚታዩ የተዛቡ አስተሳሰቦችንና የተበላሹ ወይም ዕቅደ-አልባ የአኗኗር ስልቶችን  በማጥናት ፍትሃዊነት የሰፈነበትና የእያንዳንዱ ግለሰብ መብት የሚከበርበት ስርዓት ለመመስረት ነው። በአንድ ግለሰብ ዙሪያ የሚሽከረከር ፖለቲካ ከፖለቲካ ፍልስፍናና ሳይንስ አንፃር ፖለቲካ ተብሎ ስለማይጠራ የግዴታ የአንድን ህብረተሰብ የማሰብና የመፍጠር ኃይል ያግዳል። እንያንዳንዱ ግለሰብም አምላክ የሰጠውን የማስበ ኃይል እንዳይጠቀም ስለሚገደድ የግዴታ እንደከብት እየተነዳ ይኖራል። ኑሮው ሁሉ ከከብት ስላማይሻል ህይወቱን በሚገባ ማደራጀት በፍጹም አይችልም። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በጠቅላላው ህብረተስብ ውስጥ በመስፋፋት የአንድ አገር ህዝብ ጭንቅላቱን በማስጨነቅና በመመራመር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በተፈጥሮ ላይ ቁጥጥር እንዳይኖረው ይደረጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንስቃሴ ስለማይዳብር የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት፣ ወይም በግብታዊ አስተሳሰብ የተነሳ እያቀዱ ሰፊውን ህዝብ ለመመገብ የሚያስችል የእርሻ ተግባር በማይካሄድበት አገር ውስጥ አደጋንም ሆነ ረሃብን ለመቋቋም ወይም የሚከሰተውን ረሃብ በፍጥነት ለማስወገድ የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

እስቲ አጠር መጠን ባለ መልክ ከአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የዘለቀውን በአብዛኛው መልኩ በፊዩዳላዊ ወይም በኋላ-ቀር አስተሳሰብ የተገነባውንና የተዋቀረውን ፖለቲካ ጠጋ ብለን እንመልከት። ለምሳሌ በንጉሳዊ የአገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያን የፖለቲካ አወቃቀር ለተመለከተ ፖለቲካው በሙሉ አፄ ኃይለስላሴን በማምለክ ላይ የተመሰረተ ነበር። በእርግጥ በጊዜው ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብና ተግባሩም ምን እንደሆን የሚታወቅ አልነበረም። ስለሆነም የፖለቲካ አወቃቀሩ ኢንስቲቱሽናላይዝድ ያልሆነ ወይም በተቋም መልክ ያልተዋቀረና፣ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በቤተ-መንግስቱ ዙሪያ ብቻ የሚካሄድ ስለነበር ከ95% በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያገለለና፣ በንጉሱና በዙሪያቸው ያሉት አሪስቶክራሲውና ሚኒስተሮች በሙሉ እንደልዩ ዐይነት ፍጡሮች የሚታዩና የሚፈሩ ነበሩ ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ በመፍራትና በማክበር መሀከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ መታወቅ አለበት። በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ በተቋም መልክ የተዘረጋ የፖለቲካ አወቃቀርና ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስላልነበር አብዛኛው ነገር በግብታዊ መልክ ነበር የሚካሄደው ማለት ይቻላል። ሁሉም ነገር የተመሰረተው አፄውን በማምለክና ፀሀዩ ንጉሳችን በማለት ላይ ስለነበር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እየተደራረቡ ሲከሰቱ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ተቋምና የሰለጠነ ኃይል ባለመኖሩ ህዝባችን ለከፍተኛ ረሃብና ድህነት የተጋለጠ ነበር።  ለምሳሌ በ1973 ዓ.ም በወሎ ክፍለ-ሀገር የተከሰተው ረሃብና ወደ 500 ሺህ የሚጠጋ ወገናችንን የቀጠፈው ረሃብ የዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ ዝርክርክነትና ሳይንሰ-አልባነት ያስከተለው ውጤት ነው። ስለሆነም ሁኔታው እየተባባሰና ችግሮችም እየተደራረቡ ሲመጡ የሞናርኪው አገዛዝ የግዴታ ከስልጣኑ መወገድ ነበረበት። በሌላ አነጋገር፣ አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው ከስልጣን እንዲወገዱ ሁኔታውን ያመቻቹት ራሳቸው ናቸው  ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ሲገደዱ ከፍተኛ የፖለቲካ ክፍተት ሊፈጠር ቻለ።

አፄ ኃይለስላሴ ከሰላሳ ዓመት በላይ ስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ስልጣናቸውን የሚረከብ ሰፋ ያለ የማህበራዊ መሰረት ለማዘጋጀት ባለመቻላቸው ምንም ዐይነት የፖለቲካ ዕውቀት የሌለውና በጉልበት ብቻ የሚያምን ወታደራዊ ኃይል የመንግስቱን መኪና ለመቆጣጠር ቻለ። ካለብዙም መጨነቅ የደርግን አባሎችና የተቀረውን የመኮንኖች አስተሳሰብ በምንመረምርበት ጊዜ የሰዎቹ ጭንቅላት በምሁራዊ ዕውቀት ያልተኮተኮተ ስለነበር አስተሳሰባቸው በሙሉ የጌታና የሎሌ ዐይነት ነው ማለት ይቻላል። ጭንቅላቱ በምሁራዊ አስተሳሰብ ያልተኮተኮተና ክሪቲካል አመላካከት እንዲኖረው ሆኖ ያልተዋቀረ ትዕዛዝ ከመቀበልና ከማስፈፀም፣ ወይም ራሱ ከመፈጸም በስተቀር ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በወታደሩ ውስጥ ብቻ የነበረ ሳይሆን በቴክኖክራሲውና በቢሮክራሲው ጭንቅላት ውስጥ የነበረና አሁንም ያለ በመሆኑ ስለአገርና ስለህብረተሰብ፣ እንዲሁም ስለግለሰባዊ ነፃነት የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። ስለሆነም በጊዜው ሁሉም ነገር በመንግስቱ ኃይለማርያም ቁጥጥር ስር ስለነበር አብዛኛው በእሱ ዙሪያ የተሰባሰቡት በሙሉ መንግስቱ ኃይለማርያምን የሚያመልኩ ነበሩ። በዚህ መልክ ጭንቅላቱ ባልዳበረ፣ ክርክርን በማያውቅና፣ የተለያዩ አማራጭ አስተሳሰቦችን አቅርቦ በእነሱ ዙሪያ ውይይትና ጥናት፣ እንዲሁም ክርክር በማይደረግበት ሁኔታ ውስጥ አንዱ ብዙም ሳያስብ ተነሰቶ አንድ ለየት ያለ ሃሳብ በሚያቀርብበት ጊዜ ፀረ-አብዮተኛ አስተሳሰብ ነው በማለት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ይደረጋል። በዚህ መልክ አንዳንዶች ሳያስቡት የተሻለ አስተሳሰብ በማፍለቃቸው ብቻ ህይወታቸው እንዲሰዋ ለመደረግ በቅቷል።

በሌላ ወገን በመንግስቱ ኃይለማርያም ዘመን ተራማጅ በሚባሉ ኃይሎች በመገፋት የጥገና ለውጦች እንደተካሄዱ የማይታበል ሀቅ ነው። ችግሩ ግን በጊዜው በአዋጅ መልክ የጸደቀውንና የታወጀውን የጥገና ለውጥ በስነ-ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚችል ኃይል ባለመኖሩ በፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉ ድርጅቶች፣ በተለይም መኢሶንና ኢህአፓ ወደ ግብግብ ውስጥ  ነው የገቡት። አንደኛው ሌላውን ካላጠፋሁ ለመኖር ወይም ስልጣንን ለብቻዬ ለመቀዳጀት አልችልም በማለት ወደ ርስ በስር መተላለቅ አመሩ። ይህ ሁኔታ ወደ ደርግ ውስጥ በመስፋፋቱ ፖለቲካዊ ትግሉ ወደ ርስ በርስ ጦርነት ተለወጠ። የሁለቱ ድርጅቶችን፣ ማለትም የመኢሶንና የኢህአፓን አደረጃጀት ለተመለከተ በግለሰቦች፣ ወይም በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። ተራው አባላቱ በመሪዎቹ የሚሸረበውን ወይም የሚጸድቀውን ሃሳብ በበቂው የመወያየት ዕድል አልነበራቸውም። ስለሆነም  አንዳንድ የፓርቲዎች መሪዎች እየተሳደዱ ሲገደሉ ተራ አባላቱ ምንም ግንዛቤ አለነበራቸውም። መገደልና መገዳደል እንደ ቀልድ የሚወስድበትና የጊዜው ስልትም ስለነበር እንደዚህ ዐይነቱ የወንድማማቾችና የእህትማማቾች መተላለቅን ምን ዐይነት ፋይዳ እንደሚያመጣ የሚጠይቅ አልነበረም።  ትዕዛዝ በመቀበል የዚህ ወይም የዚያኛውን ፓርቲ አባል ሳያወጡና ሳያወርዱ ህይወቱን መቅጠፉ ዋናው የፖለቲካ ስልት ስለነበር በዚህ ዐይነቱ አሳዛኝ ድርጊት የማይዝናና ወይም የማይደሰት አልነበረምን፤ የሚታየውም እንደ ጀግንነት ነበር። ፖለቲካ ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ ´ስውን መግዲያ መሳሪያ ወደ መሆን ስለተለወጠ የኋላ ኋላ የተረፈው መበታተን ሆነ ዕጣው። እንደሚታወቀው ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን ህብረተሰባዊ ችግሮችን መፍቻ እንጂ ሰውን መግደያና አገርን ማከረባበቻ መሆን ባልተገባው ነበር። ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ያልተዋቀረ ጭንቅላት ደግሞ  ድርጊቱ በሙሉ በአርቆ-አሳቢነት ላይና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ ስለሚሆን አመራሮች በደርግ ሲመቱ ድርጅቶቹ እንዳሉ ለመበተን በቁ፤ እንደምናየው የታሪክ ትዝታ ለመሆን በቁ። መንግስቱ ኃይለማርያምም ተገዶ ስልጣንን ሲለቅ ወታደሩ ለመበታተን ተገደደ።

ህወሃት የሚባለው የጎሳና በጥላቻ፣ እንዲሁም በቂም በቀል ላይ የተመሰረተ የባንዳ ልጆች ስብስብ በአሜሪካንና በእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ ስልጣንን በመጨበጥ አዲስ ታሪክ መስራት አለብኝ በማለት አገርን ማፈራረስ ጀመረ። ሀወሃትም ራሱ በመለሰ ዙሪያ ብቻ የተደራጀ ስለነበር መለስ ከሞተ በኋላ ብዙም መራመድ አልቻለም። ከመለሰ በታች የነበሩት፣ እነ ስብሃት ነጋና ሌሎች በሙሉ የደንቆሮዎች ስብስቦች ስለነበሩ ስለፍልስፍና፣ ስለአንትሮፖሎጂ፣ ስለተፈጥሮ ሳይንስ፣ ስለፖለቲካል ኢኮኖሚክስ፣ ስለሶስዮሎጂ፣ ሰለከተማ ዕቅድና እንዲሁም ስለተለያዩ አንድን ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ ማደራጀት ሰለሚያስችሉ ነገሮች ምንም የሚያውቁት ነገር ስላለነበር በውጭ ኃይሎች እየተመከሩ ለሰፊው ህዝብ ምንም የማይጠቅመውን ትላልቅ ህንፃዎች  በማሰራት የከተማን ዕድገት የሚያበላሹብና የህዝቡም አስተሳሰብ እንዲዘበራረቅ የሚያደርጉ ነበሩ። ከዘረፋና ራስን አደልቦ በውስኪ ከመታጠብና ጥሬ ስጋ ከመብላት በስተቀር የሚያውቁት ነገር ስላልነበር በዕውቀት አካባቢ አንድም የተሰራ ነገር አልነበረም። ሆቴልቤቶችን ከማስፋፋትና ታዳጊ ወጣቱን ከማባለግ በስተቀር በየቀበሌውና በአገሪቱ በመላው የወጣቱን መንፈስ የሚያርቁ ቤተ-መጻህፍትና የዕውቀት ማዕከሎች በፍጹም አልተገነቡም። ሁላችንም በሚገባ እንደምናውቀው ዕወቀት ባልተስፋፋበት አገር ውስጥና ፖለቲካው በተቋም መልክ ባለተገነባበት አገር ከአርቆ-አሳቢነት ይልቅ አርቆ-አለማስብ በማየል ሁሉንም ነገር በኃይል ለመፍታት ይሞከራል። በዚህ መልክ የሚካሄድ ፖለቲካ ደግሞ የውጭ ኃይሎች መጫወቻ ይሆናል። ህወሃት ወይም ወያኔ በ27 ዓመት የስልጣን ዘመኑ የውጭ ኃሎች አሻንጉሊት በመሆን በአገራችን ምድር በፍጥነት የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ነው ያደረገው። ስልጣኑንም ከለቀቀ በኋላ እነ አሜሪካና ግብረአበሮቹ የሙጥኝ ብለው የሚደግፉት እነሱ የሚፈልጉትን አንድን አገር የማባለግ፣ ህዝብን የማደንቆርና የማደኽየት ስራ ሰለሚሰራላቸው ነው። በአሜሪካኖችና በግብረአበሮቹም ሁልጊዜ የሚደገፈው፣ የሚፈለገውና ሽር-ጉድ የሚባልለት እንደዚህ ዐይነቱ ብሄራዊ ነፃነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማይገባውና፣ ብሄራዊ ክብርን ለማስጠበቅ የማይጨነቀውን ደንቆር ኃይል ብቻ ነው። አንድን ህዝብ እያደኸየና አገርንና ህዝብን እያስናቀና እያወረደ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚፈልገውን ኃይል ብቻ አሜሪካና የተቀሩት ግብረ-ኧበሮቹ የሚፈልጉት። የእነሱ ምኞት በተለይም ጥቁር የሚባል ፍጡር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ አገርን የሚያስከብር ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚካሄደው ትግል ይህ ነው። የበላይነትን በሁሉም አገሮች ውስጥ ማስፈንና የጥሬ ሀብታቸውን መበዝበዝ ነው የኢምፔሪያሊስት አገሮች ዋናው የፖለቲካ ስልታቸው። የተወሳሰቡ የመሸወጃ መሳሪያዎችንና ዘዴዎችን በመፍጠር የሶስተኛው ዓለም ኤሊቶችን እንደፈለጋቸው እያሽከረከሩና በአገሮች ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር እያደረጉ ነው።

 የዛሬው የአገራችንም ሁኔታ በዚህ መልክ ነው መረዳት የሚቻለው። ሁሉንም ነገር በአቢይ ዙሪያ የሚሽከረከርና በእሱ ፈቃድ ብቻ የሚካሄድ ነው። አቢይ ፈጣሪም አድራጊም የሆነ ብቸኛው ግለሰብ ነው። ስለ ህግ የበላይነት የገባውና በዚህም የሚተዳደር አይደለም። ፈላጭ ቆራጭ የሆነና ትችትንም የማይቀበል፣ ትችት ከተደረገበትና የሚጠየቅ ከሆነ ደግሞ ሁኔታው ሲመቻችልት ያፋጠጠውን ሰው የሚያሰቃየውና ወደ እስር ቤትም እንደሚያስወረውረው ነው። አቢይ አህመድ እንደ አጋጣሚ ስልጣን ላይ ከወጣ፣ ትንሽ ጊዜያት ከቆየና ብዙዎችን ካታለለና በዙሪያው እንዲሰበሰቡ ካደረገ በኋላ አገራችንና ህዝባችንን ቀስ በቀስ አዘቅት ውስጥ ነው የከተታቸው። ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማፈንና የሚጋፈጡትን በሙሉ በማስወገድ አምባገነንቱን አጉልቶ ለማውጣት የቻለ እጅግ አደገኛ ሰው ነው። ባለፉት አራት ዓመታት በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እንዲፈናቀሉና እንዲገደሉ ተደርገዋል። በተለይም ከስድስት ወራት ጀምሮ በአማራው ክልል የሚደረገው ጦርነት የሚያረጋግጠው አቢይ አህመድ መንፈስ አልባ የሆነና አረመኔ መሆኑን ነው። በአካባቢው ድርጊቱን የሚቃወምና ተው የሚለው ሰው ስሌለ ሁሉም አፋቸውን ከፍተው ነው ሲዘላብድ የሚመለከቱት። ይህም የሚያረጋግጠው ሚኒስተሮችም ሆነ ጄኔራሎች ተብዬዎች ዕውቀት የሌላቸውና በራሳቸው የማይተማመኑ ብቻ ሳይሆኑ፣ አገርና ህዝብ፣ እንዲሁም ግለሰብአዊ ነፃነት ምን እንደሆኑ ያልገባቸው እንደሆኑ ነው። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ፋሺሽታዊ አገዛዝ መመስረቱና አገሪቱን ማመሱ የሚገርም ጉዳይ አይደለም። ይህ በራሱ የሚያረጋግጠው በአገራችን ምድር የቱን ያህል ምሁራዊ ክፍተትና በዕውቀት የተካነ ከበርቴያዊ ኃይል አለመኖሩን ነው። በዚህ መልክ የተዋቀረ አገዛዝና የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት በተሳሳተ ትረካ ላይ በመመርኮዝ ታሪክንና ባህልን እንደሚያበላሽና አገርን እንደሚያመሰቃቅል እያየን ነው። ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ አገዛዝ ሲወገድ ደግሞ ያበላሸውንና ያዘበራረቀውን የፖለቲካ ሁኔታ ለማስተካከል ከፍተኛ ዕውቀትንና ጥበብን ይሻል። በተራ የአካዴሚክስ ዕውቀት የሚፈታ አይሆንም ማለት ነው።

ከዚህ ወጣ ብለን የሌሎች ድርጅቶችንም ሁኔታ፣ ቀድሞ ግንቦት ሰባት፣ በኋላ ደግሞ የአዜማን ሁኔታ ስንመለከት ሁሉም ነገር በብርሃኑ ነጋ ዙሪያ የሚሽከረከርና አባላቱ በሙሉ የሚፈሩት ናቸው። ለምሳሌ ብርሃኑ ነጋ  በምን ቅድመ-ሁኔታና ማን ፈቅዶለት የትምህርት ሚኒስተር ለመሆን እንደበቃ የሚታወቅ ጉዳይ የለም። ፓርቲው ሳይልከውና በበቂው ሳይከራከሩበት ነው አቢይ ሚኒስተር ሁን ስላለው ተሽቀዳድሞ ስልጣንን የተቀዳጀው። ብርሃኑ ነጋ ግንቦት ሰባትን ሲመሰርትና ሲንቀሳቀስ አባላቱ ሰፋ ያለ ዕውቀትን እንዲቀስሙና ተተኪዎችም እንዲፈጠሩ ያደረገው ምንም ዐይነት ጥረት አልነበረም። በየጊዜው ሳይንሳዊ ጥናቶችም አያካሄዱም ነበር። በደንብ የተደራጀ ድረ-ገጽና በየሳምንቱ የሚታተም ጋዜጣም አልነበራቸውም። ዝም ብለው ብቻ ሰፊውን ተከታዮቻቸውን በማታለልና በተራ ወሬ ገንዘብ በመሰብሰብ ብቻ ነው ጊዜያቸውን ያባከኑትና ብዙዎችንም አደንቁረው ያስቀሩት፤ የሰሩትም ተጨባጭ ስራ አልነበረም።  አብዛኛው ተከታዮቻቸውም የጠለቀ ዕውቀት ስላልነበረቸውና ስለሌላቸው ብርሃኑ ነጋ የሀብታም ልጅ ስለሆነና በሰውነቱ ስለሚተማመን ሁሉም እንደ አምላክ የሚያከብረው ነበር ማለት ይቻላል። እንደነ ነዓምን ዘለቀ የመሳሰሉ ጠለቅ ያለ ዕውቀት የሌላቸው የሰውየውን አካሄድ የመቆጣጠር ችሎታ አልነበራቸውም። የግንቦት ሰባት መሪዎች እንዳሉ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተላላኪዎች ስለነበሩ የዕውነተኛ ነፃነትና የዲሞክራሲ ስርዓት አራማጆች አልነበሩም ማለት ይቻላል። ይታገሉ የነበሩትም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅመውንና ከድህነት ሊያላቅቀው የሚችለውን ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ሳይሆን፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮች የምትታሽና ለዝንተ-ዓለም በድህነት እየማቀቀ የሚኖርባት ህዝብና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትተላለፍ የምትሆንን አገር ነው።  የግንቦት ሰባት ሰዎች ዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ያልገባቸው የአድርባዮች ስብስብ  ነው ማለት ይቻላል። በዛሬው ወቅት ብርሃኑ ነጋም ሆነ የድሮዎች አምላኪዎቹና ተከታዮቹ ያሉበትን ሁኔታ በደንብ እየተመለከትን ነው። የሚያሳዝነው ነገር እንደነዚህ ዐይነት በምሁራን ስም የሚነግዱ ግለሰቦች አንድን ህዝብ ሲያሳስቱና አገርን እንዲበታተን ሁኔታውን ሲያመቻቹ ቀደም ብሎ ለመገንዘብ የሚያስችል ዕውቀት አለመኖሩ ነው። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችም ትምህርትንና የምሁራንን ስም እንዳለ ለማጉደፍ ችለዋል። የመማር ትርጉሙ ታዲያ አገርን ለመበታተን ነው ወይ? እያለ የማይጠይቅ የለም። ሌላው ደግሞ እያወቁ ነው የሚያደርጉት፣ ዕውቅትስ አላቸው የሚል አለ። እንደዚህ ብለው የሚከራከሩ ሰዎች በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ በተመሰረተው ዕውነተኛ ዕውቀትና በተራ አካዴሚስክ መሀከል ያለውን ትልቅ ልዩነት የማይረዱ ናቸው።  አንዳንዶች በጊዜው ከትክክለኛ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ሁኔታ በመነሳት ትችት ሲያቀርቡ የፍየል ወጠጤ ይዘፈንብሃልና አርፈህ ተቀመጥ በማለት የዛቻ ድምፃቸውን ያሰሙ እንደነበር የሚታወቅ ነገር ነው።

ወደፊት የሚፈጠረውም የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ በግለሰቦች ዙሪያ የሚሽከረከርና ህዝባችንን ዕውነተኛ ነፃነት የማያጎናፅፈው የመሆን አደጋው ከፍ ያለ ነው። በአገር ቤት ውስጥ በፋኖዎች የሚደረገው ቆራጥ ትግል ሙሉ በሙሉ የሚደገፍ ቢሆንም፣ ይህ ዐይነቱ ብዙ መስዋዕትነትን የጠየቅውና የሚጠይቀው ትግል በተለይም በውጭው አገር፣ አሜሪካ በተሰባሰቡና አማራውን እንወክለዋለን በሚሉ፣ በመሰረቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተላላኪዎች በሆኑና ባልተገለጸላቸው ግለሰቦች የመጠለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።  እነዚህ ታዋቂ ነን የሚሉ ግለሰቦች ሰለፖለቲካ ኢኮኖሚክስ፣ ሰለፍልስፍና፣ ሰለተፈጥሮ ሳይንስ፣ ስለሶስዮሎጂ፣ ሰለ ኤስቴቲክስና፣ አንድን አገር በተሟላና በተስተካከለ መልክ ስለሚያገነባውና ህዝቡንም እንዲተሳሰር ስለሚያደረገው ዕውቅት ይህን ያህልም ግንዛቤ የሌላቸው በመሆናቸው አገራችንና ህዝባችን ለብዙ አስርት ዓመታት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አሽከር ሆነው እንዲቀሩ ያደርጓቸዋል። የተከበረች፣ ህዝቦቿ ሙሉ በሙሉ ነፃነታቸውን የሚጎናጸፉባትና እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ የተከበረችና የምታምር ኢትዮጵያን እንዳይገነቡ ይደረጋሉ ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ እንደነዚህ ዐይነት ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ስልጣን ላይ እንዳይወጡና ስንትና ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል መና ሆኖ እንዳይቀር ከአሁኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዕውነተኛ ነፃነትና ለተከበረች አገር ለመታገል የሚፈልግ በግልጽ በማንኛውም አገርን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ መወያየት አለበት። ሁሉም ነገር በሳይንስ መነፅር መመርመር አለበት። የአንድ አገር ችግር በሳይንስና በፍልስፋና  ዕውቀት ብቻ የሚፈታ እንደመሆኑ መጠን የግለሰብ ፍላጎት ቦታ አይኖራቸውም። ምክንያቱም አንድ አገር ከአንድ ትውልድ ወደሚቀጥለው ካለምንም ውዝግብ መተላለፍ አለበት ተብሎ የሚታመን ከሆነ ከዕውቀት ውጭ በፖለቲካ ስም የሚደረግ ማወናበድ ለዝንተ-ዓለም አገርን እያተራመስ ይኖራል ማለት ነው።

ባጭሩ ግለስቦችን በማምለክ ላይ የሚመሰረት ድርጅት የመጨረሻ መጨረሻ ይፈራርሳል፤ ለአገርም ከፍተኛ ጠንቅ ጥለው ነው የሚያልፉት። የፖለትካ ትርጉሙም እንዲጠፋ ነው የሚያደርጉት። አገርን አጨልመውና ህዝብን ለአደጋ ጋርጠው ነው ጥለው የሚያልፉት። በመሆኑም ምሁራዊና ሳይንሳዊ ይዘት የሌለውና ሰፋ ባለ መልክ ያልተደራጀ፣ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀስ የመጨረሻ መጨረሻ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ክፍተትን ጥሎ ነው የሚያልፈው። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ማንም እየተነሳ ፖለቲከኛ ነኝ በማለት ሰፊውን ህዝብ ማወናበድ ይጀምራል። ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ነገር በሰፊው ካልታሰበበትና በምሁራዊ ዕውቀት ላይ ተመስርቶ በተቋም መልክ ካልተገነባና ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ ካልሆነ አንድ አገር የመበታተን ኃይሉ ከፍ ይላል ማለት ነው። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                                                          fekadubekele@gmx.de

                              www.fekadubekele.com

                     https://open.spotify.com/episode/75ma9vTCC3qLLCxnsfB3Wf

                                        https://www.youtube.com/watch?v=6bqggd_mIkg