[gtranslate]

ለመሆኑ ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህን  በምን ምክንያት ነው የክብር ዶክትሬት

ዲግሪ የተሰጣት?  አገር ስለቸበቸበች ወይስ ሁለ-ገብ ዕድገትን ስላመጣች?

                                                       ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                             ታህሳስ 7 2021

 

እ.አ በ21.11.2021 በኢትዮጵያ ምድር “የአገዛዝ ለውጥ” ሊመጣ የሚችልበትን ሁኔታ አስመልክት የቀድሞው የአሜሪካን አምባሳደር በኢትዮጵያ ዶናልድ ያማሞቶ፣ የቀድሞው የታላቋ ብሪታንያ አምባሳደር በኢትዮጵያ፣ ሮበርት ዴዋ፣ የቀድሞዋ የፊንላንድ አምባሳደር በኢትዮጵያ ክሪስቲ አአርኒኦ፣ የቀድሞው የፈረንሳይ አምባሳደር በኢትዮጵያ፣ ስቴፋን ጎምፔርትዝ፣ በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ውስጥ የአፍሪካ ተጠሪ የሆነችው ቪኪ ሁድደስን፣ ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃክ፣ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን፣ የትግራዩ ተወካይ ከሆነው ብርሃኔ ገብረክርስቶና፤ እንደዚሁም ከሌሎች ትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ፣ ግን ደግሞ የአሜሪካን ዜግነት ካላቸው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በሰላምና በዕድገት ሽፋን ስም ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ተወያይተዋል። በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት ውስጥ ስማቸው ጎልቶ የወጣውና መነጋገሪያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ኢስሃክና የኮሞዲቲ ገበያ መስራች የነበረችው ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህን ናቸው። ፕሮፌሰር ኤፍሬም ኢስሃክ እ.ኢ አ ከምርጫ 1997 ዓ.ም ተያይዞ በተደረገው ውዝግብና የምርጫ ውጤት ሰረቃ ጋር የቅንጅት መሬዎችን ከእነ መለስ ዜናዊ ጋር ለማስታረቅ ሽር ጉድ ሲሉ ስማቸው ሲነሳ እንደነበር ይታወቃል። ፕሮፌሰሩ የፖለቲካ ሰው ሳይሆኑ ምሁር በመሆናቸውና ሸምገል ያሉ ስለሆኑ በአስታራቂነት የተመረጡ እንደነበሩ ይታወቃል። ይሁንና ሰሞኑን በዕድገትና በሰላም ሽፋን ስም በተደረገው የአገዛዝ ለውጥ ስብሰባ ላይ ለምን እንደተገኙና ዓላማቸውስ ምን እንደሆነ በፍጽም የሚታወቅ ነገር የለም። እኔም ራሴ እዚህ በርሊን በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ ሰምቻቸው ስለነበር፣  ስለ ዓለም አቀፍም ሆነ ስለአገራዊ ፖለቲካ ያላቸው ግንዛቤ ይህን ያህልም እንዳልሆነ ለማወቅ ተገንዝቢያለህ። ስብሰባው ስላልጣመኝና በአገላለጽም ስላልረካሁ ስብሰባው ከማለቁ በፊት ነው ጥዬ የወጣሁት።

ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህን  እ.አ በሚያዚያ ወር 2008 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ምድር የኮሞዲቲ ገበያ ሲመሰረት እንደዋና መስራች በመሆን የዎል-ስትሪትን የወከለች በሚመስል መልክ ነው የአለቃነት ቦታ የተሰጣት። ቴድ( TED) በመባል በሚታወቀው በአመሰራረቱ ከቴክኖሎጂና ከዲዛይን ጋር በተያያዘ የተመሰረተ የመወያያ ወይም ዕውቀትን ማስተላለፊያ መድረክ ላይ ሆና ስለገበያ ኢኮኖሚ፣ ስል ኢንተርፕኔየርሺፕና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የገበያ ኢኮኖሚ ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ፣ በጥሩ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣  ይሁንና ደግሞ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ በሆነ መልክ በሌክቸር መልክ ስትሰጥ የማዳመጥ ዕድል አጋጥሞኛል። እሷ ብቻ ሳትሆን በገበያ ኢኮኖሚ የተሳከሩ፣ ይሁንና የካፒታሊዝምን ዕድገት በደንብ ያላጠኑ፣ አንድ ሰሞን አዲስ አበባ እየተመላለሱ በሁለት ሰዓት ሌክችር እስከ $ 12 ሺህ ዶላር እየተከፈላቸው  በተለይም ስለገበያ ኢኮኖሚ ዕድገትና ውስጣዊ አሰራር የማያውቁ፣ የገበያ ኢኮኖሚ የንግድነት ልውውጥ ብቻ የሚካሄድብትና ትርፍ የሚካበትበት የሚመስላቸውን ነጋዴዎችንና ወጣቶችን መንፈስ በመመረዝ ቲአትር ሲሰሩ የማዳመጥና የመመልከት ዕድል አጋጥሞኛል። እንዳንድ ከአሜሪካን የሄዱ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች አንድን ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ሚሊዮኔር ለማድረግ ይቻላል እያሉ ከዕውነት የራቀ ሀተታ ሲሰጡ ለመከታተል ችያለሁ። ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ተገዶ ስልጣኑን እስካስረከበ ድረስ በኢትዮጵያ ምድር በገበያ ኢኮኖሚ ስም ከፍተኛ ወንጀል ተሰርቷል። ከላይ እንዳልኩት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ተላላኪዎች በመሆን የምግብና የሆቴል ማደሪያ ሳይጨመርበት በሁለት ሰዓት በፓዎር-ፖይንት በታጀበ ፍሬከርሲ ገለጻ እስከ $12 ሺህ ዶላር እየተከፈላቸው በዙ የዋሆችን አሳስተዋል። ከዚህም በላይ በብሄራዊ ባንክ ውስጥ በአማካሪነት የሚሰራ ኢትዮጵያዊ የዓለም የገንዝብ ድርጅት(IMF) ልኮት እዚያው ተቀጥሮ እንዲሰራ በማድረግ እስክ $10 ሺህ ዶላር በየወሩ እንዲከፈለው በማድረግ ትልቅ ወንጀል ይሰራ ነበር። ይህ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ወክሎ የሚሰራው ኢትዮጵያዊ ደሞዙን የሚከፍለው የወያኔ መንግስት ሲሆን፣ በስራው ዓለም ላይ በነበረበት ጊዜ የሰራው ምንም ነገር አልነበረም። ተከታትዬ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ሰውዬው ውሎው ሼራተን ሆቴል እንደነበረና፣ የኋላ ኋላ በስራው ያልተደሰቱ የባንኩ አስተዳዳሪዎች ደሞዙን ከ10 ሺህ ዶላር ወደ አንድ ሺህ ዶላር እንደቀነሱበት ለመስማት በቅቻለሁ።

ያም ሆነ ይህ እንደነዚህ ዐይነት የገበያ ኢኮኖሚ አራማጅ ነን የሚሉ ኢኮኖሚስቶች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያና ብሄራዊ ኢኮኖሚ እንዴት እንደሚገነባ ሳይሆን፣ በንግድ አማካይነትና በቱሪዝም ብቻ ለውጥ ይመጣል እያሉ በማስተማር አገዛዙንም ሆነ ኢኮኖሚስቶችንና፣ በኢንዱስትሪና በንግድ ቻምበር ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎችን ሁሉ ለማሳሳት ችለዋል። በተለይም የተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት እንደኛ ባለ አገርና በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ስለካፒታሊዝምና ስለገበያ ኢኮኖሚ አፀናነስ፣ አስተዳደግና በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ አምራችነት ወደ ተወሳሰበና በደንብ ወደ ተደራጀ የኦሊጎሎፖሊስትና የሞኖፖሊ ካፒታሊስት ስርዓት እንዴት ለመለወጥና  ዓለምን ሊቆጣጠር እንደቻለ በሌክቸር መልክ በማይሰጥበት አገር በተለይም ወጣቱን ትውልድ ለማሳሳትና መንፈሱን ገንዘብ በማግኘት ብቻ እንዲመረዝ ለማድረግ ይቻላል። ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ምርታማነት፣ ውድድርና የስራ-ክፍፍል ሳይሆኑ የካፒታሊዝም ውስጣዊ ኃይል አንቀሳቃሺዎች፣ ንግድና በችርቻሮ ላይ ብቻ በመሰማራት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል ተብሎ በሚሰበከበት አገር የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማደለብ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን ህዝብ ደግሞ ማድኸየትና አቅመ-ቢስ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ስልጣንን ይዞ አገርን ሲመዘብር፣  የብልግና ኢንዱስትሪ ሲያስፋፋና አገራችንን የቆሻሻ መጣያ ሲያደርግ ይህንን ዐይነቱን በሳይንስ ያልተደገፈ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ነው።

ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህንም የኮሞዲቲ ገበያ ዋና ኃላፊ ሆና ስትመረጥ ዋና ዓላማዋም በአገራችን ምድር ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴኮኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንውን እንዲዳብርና የውስጥ ገበያ(Home Market) እንዲስፋፋ ለማድረግ ሳይሆን፣ በተለይም በቡና ምርት ላይ የተሰማራውን አምራች ገበሬ ሌሎች ለምግቡ የሚሆኑ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን፣ እንዲሁም አትክልቶችን በማብቀል ራሱን ሊመግብ እንዳይችል በማድረግ የባሰ ተበዝባዥና በአንድ የአመራረት ሰብል ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲሆን ማድረግ ነው። በዚህም አማካይነት በገጠር ውስጥ ድህነትን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በርሱ የተያያዘ የአመራረትና የንግድ ልውውጥ እንዳይዳብር ማድረግ ነው። በአንድ አካባቢም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ የስራ-ክፍፍል ካልዳበረ፣ በገንዘብ አማካይነት የንግድ ልውውጥ ካልተካሄደ፣ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ሰፋ ያለ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ግልጽነት ያለው ብሄራዊ ኢኮኖሚ ማሳደግ በፍጹም አይቻልም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በምርት ኢኮኖሚ ሳይሆን በንግድ ኢኮኖሚ የሰለጠኑንና የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ህግና አሰራር በደንብ የማያውቁ ከዎል-ስትሪት ተልከው እንደኛ ያለችው አገር ሲመጡ ዋናው ተልዕኮአቸው ውስጣዊ ኃይልና ግልጽነት ያለው የገበያ ኢኮኖሚ እንዳይዳብር ማድረግ ነው። እንደ ሼራተንና ስካይላይን በመሳሰሉ የመባለጊያ ሆቴል ቤቶች በመገናኘትና በመደራደር ሰፊውን ህዝብ የባሰ ደሃ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በከፍተኛ ደረጃ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ በማድረግ ወጣቱና ታዳጊው ትውልድ ጭንቅላቱ እንዲስለብ በማድረግ ባህልና እሴት እንዲወድሙ ማድረግ ነው።

በዚህ መንፈስ የታነፀችው ዶክተሯ ዋና ስራዋ፣ ስራዋን ከጀመረችበት ቀን ጀምሮ የተያያዘችው የወያኔ ሰዎች በሀብት እንዲካብቱ ማድረግ ነው። ቀደም ብለው የወያኔ ካድሬዎች እንደሰሊጥ የመሳሰሉትን የቅባት እህሎችን፣ ዕጣንና ሌሎች የማዕድን ሀብቶችን ይቆጣጠሩ እንደነበረው፣ በዚህ ዐይነቱ የኮሞዲቲ ገበያ ብለው በሚጠሩት አማካይነት ሀብትን ከማከማቸት አልፈው ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀም በመልመድና በመባለግ አገራችንን የዝሙት ገበያ ለማድረግ በቅተዋል። እንደ ግብረ-ሶደማዊነት የመሳሰሉት አፀያፊ ተግባሮች እንዲስፋፉ ለማድረግ በቅተዋል። ወይዘሮዋ በዚህ መልክ በቀጥታ ባትሳተፍም ኢ-ሳይንሳዊ፣ ኢ-ሞራላዊና ኢ.-ስነምግባራዊ የሆነ ምርታዊ ክንዋኔን ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም የኮሞዲቲው ገበያ በቀጥታ ከዎል-ስትሪት ጋር እንዲያያዝ በማድረግ ብዙ ሀብት ወደ ውጭ ሊወጣ የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከፍተኛ አገራዊና ህዝባዊ ወንጀል ለመፈጸም ችላለች። እንደሚታወቀው የአንድ አገር ወዳድ ኢኮኖሚስት ዋና ተግባር ወደ ውስጥ ያተኮረ ገበያ እንዲያድግ አመቺ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ወደ ውጭ ሊሸጥ የሚችል ምርት በፋብሪካ ውስጥ ሳይፈበረክና እንደመጨረሻ ምርት(End Product) ሳይመርትና ሳይታሸግ እንዳይላክ ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው እርስ በርሱ የተያያዘ የምርት ክንውን(Value-added chain) ሊፈጠርና ብሄራዊ ኢኮኖሚ ሊዳብር የሚችለው። ከዚህ ዐይነቱ አገርን የማዳከም፣ ህዝብን የማድኸየትና ሀብት እንዲዘረፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ እንዳያድግ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለተሳተፈችና ሁኔታውን ላመቻቸች ሴት የአዲስ አበባም ሆነ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትነት ማዕረግ አበርክተውላታል፤ የሚያሳዝንም የሚያስቅም ነገር ነው!

ይህ የሚያሳየን ምንድነው? በአገራችም ምድር የተቋቋሙት ዩኒቨርሲትዎችና በውስጣቸው የሚያስተምሩት ምሁራን አንድን አገር በተሟላ መልክ ለማሳደግ የሚያስችል ምሁራዊ ብቃትነት እንደሌላቸው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በገበያ ኢኮኖሚ ስም የሚፈጸመውን ወንጀል ጠጋ ብለው ለመመልከት፣ ለማጥናትና ለመመራመር የማይችሉና ሁኔታውም ሊታረም የሚችልበትን ሁኔታ የተሻለ ትንተና ለመስጠት እንደማይችሉ ነው። አንድ ሰሞን ኢትዮጵያ የዓለም ንድግድ ድርጀት(WTO) አባል መሆን አለባት ተብሎ ማመልከቻ ሲቀርብና ዝግጅት ሲደረግ፣ ይህ ሊሆን እንደማይችል፣ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለች ደሃ አገር የዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና ቴክኖክራታዊ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት የግዴታ የውስጥ ገበያ ማሳፋፋትና ማዳበር እንዳለባት፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት የበለጠውን ድርሻ የሚይዘው የእርሻ ውጤት ስለሆነና፣ ኢኮኖሚዋም የበለጠ የችርቻሮ መልክ በያዘበት ሁኔታ ውስጥ የንግድ ድርጅቱ አባል መሆን የባሰ በዚያው እንድትቀጥል እንደሚያደርጋት ሰፋፊ ሀተታዎቼን ያነበቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዚህ መልክ እንደማይማሩና አንዳንድ ዶኩሚንቶችም እንድልክላቸው ጠይቀውኝ በመላክ ግንዛቤዎች እንዲኖራቸው ለማድረግ ሞክሬአለሁ። በተለይም ስለ ዕድገት ኢኮኖሚ የሚያስተምረውን የኢኮኖሚክስ ዴፓርትሜንት ለመገናኘት ያደረግሁት ሙከራ ምንም ውጤት አላመጣም። መጽሀፌንና በብዙ ገጾች የሚቆጠሩ ጽሁፎቼን ብልክም ምንም ዐይነት አዎንታዊ መልስ ለማግኘት አልቻልኩም። በተለይም የዓለም ንግድ ድርጅትን አባል የመሆን ጉዳይ አስመልክቶ ቻይና በ2005 ዓ.ም የንግድ ድርጅቱ አባል ከመሆኗ በፊት የተጓዘችበትን የውስጥ ጥንካሬ በማሳየት አገራችንም የግዴታ የቻይናን ምሳሌ በመከተል በመጀመሪያ ደረጃ  በሁሉም አቅጣጫ ኢኮኖሚው መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ሂደት መሆኑን ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ከውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚን የመገንባትን ሂደትና በዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ውስጥ መሳተፍንና ገበያውን ከውጭ ለሚመጣ ዕቃ ክፍት ማድረግ በታወቁት የጀርመን የብሄራዊ ኢኮኖሚስት ምሁራን እንደነ ፍሪድሪሽ ሊስት በመሳሰሉት ይነሳ የነበረውን ተቃውሞና ሳይንሳዊ ሀተታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና፣ እንደነ ጀርመን የመሳሰሉት አገሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ጃፓንም ሆነ ደቡብ ኮርያ በመጀመሪያ ደረጃ ቅድሚያ የሰ›ጡት የውስጥ ገበያን ማዳበርና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነትን ማግኘት እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። የእኔ ሀተታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አመርቂና ሳይንሳዊ ጥናቶች እያሉና ተጨባጩም ሆነ የአንዳንድ አገሮች ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ቀደም ብሎ በአቶ መለሰ ዜናዊ፣ በኋላ ደግሞ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የኢትዮጵያ አገዛዝ ለነገሩ ደንታ ባለመስጠት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ካልሆን እንታነቅለን እያሉ ሲራወጡ ነበር። ዶ/ር አቢይም ስልጣንን ከተቀዳጁ በኋላ አማካሪዎቻቸው ሆን ብለው የያዙት የእነ አቶ መለስንና የእነ አቶ ኃይለማርያምን ደሳለኝ ፈለግ መከተል ነው።

ይህንን ትተን ወደ ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህን ሁኔታ ስንመጣ ከላይ ለማተት እንደሞከርኩት በዚህ መልክ የሰራችው ወንጀሏ ሳይበቃት፣ የአገራችንን ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ እንዲመሰረት እንዳደረገች፣ የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ እንዳደረገች፣ የስራ-ክፍፍል እንዲዳብር አመቺ ሁኔታዎችን እንዲፈጠር ለማድረግ እንደቻለች፣ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንደ አሸን እንዲፈልቁ ጥናትና ምክር እንደለገሰች፣ የባንኩ ዘርፍ የውስጥ ሀብትን ወይም ገንዘብ ሊሰበሰብና የክሬዲት ስይስተም ሊፈጥር የሚችልበትን ሁኔታ… ወዘተ. ወዘተ. ለማመቻቸት እንደቻለችና ብቃትነቷንም እንዳስመሰከረች ሁሉ ዶ/ር አቢይ ስልጣንን ከተረከቡ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስተሩ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ሆነው ከተመረጡት አስራአራት የኔዎ-ሊበራል ወይም የንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ አቀንቃኞች ውስጥ አንዷ ነበረች። ከእነዚህ ውስጥ ቀድሞ ዓለም ባንክ ውስጥ ይሰራ የነበረው ዶ/ር ዮናስ ብሩ የሚባልና፣ እንደነ ፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን የመሳሰሉትና፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ እንደነ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ የመሳሰሉት ኢኮኖሚስቶች ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ ለየት ያለ አመለካከት፣ ለምሳሌ ኬይኔሲያን ኢኮኖሚስት፣ የማርክሲስት ኢኮኖሚስት፣ ኢንስቲቱሽናልና የፊዚካል ኢኮኖሚስት አዋቂዎች አይገኙበትም። ፈላስፋዎችና ሶስይሎጂስቶችም አልተካተቱበትም። የጠቅላይ ሚኒስተሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው የተመረጡት በተለይም ወያኔ 27 ዓመታት ያህል አገሪቱን ሲገዛ በነበረበት ዘመን በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ በመመከር ተግባራዊ ያደረገውን የተቅዋም ማሻሻያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Structural Adjustment Program) አስመልክቶና ያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ፣ ለምሳሌ እንደዋጋ ግሽበት የመሳሰሉትን፣ የንግድ ሚዛን መዛባትና ኢትዮጵያ ከውጭ የምትበደረው ገንዘብ በየዓመቱ እያደገ ስለመምጣቱ ጉዳይና፣ በተለይም ደግሞ በእንደዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ድህነት ለመቀረፍ ያልተቻለበትንና ምክንያቱንም አስመልክተው የጻፉት ምንም ነገር የለም። ማለት የሚቻለው  የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው የተመረጡት ኢኮኖሚስቶች በሙሉ በተለያዩ ጊዜያት የአፍሪካን ኢኮኖሚ መልክ ለማስያዝ በሚል ሰበብ በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክና፣ ባጭሩ በዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው በየአስር ዓመቱ የሚዘጋጀውን አሳሳቸ ስብሰባ አስመልክቶ ክሪቲካል በሆነ መልክ የጻፉት ምንም ነገር የለም። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አዲስ የተፈጠረውን የኃይል አሰላለፍና፣ ይህንን ተገን በማድረግ በገበያ ኢኮኖሚ ስም በተለይም በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የተስፋፋውን የህበት ዘረፋ፣ ባልተስተካከለ ንግድና(Unequal Exchange) በዕዳ አማካይነት ከአፍሪካ ወደ ካፒታሊስት አገሮች ሀብት የሚሸሽበትን ወይም የሚፈስበትን ሁኔታ አስመልክቶ ትችታዊ በሆነ መልክ የጻፉና ያስተማሩ አይደሉም። የኢኮኖሚ ዕርዳታ የሚባለውም ነገር የሚያስከትለውን ጠንቅ አስመልክቶ የሰጡት ሀተታ የለም።

እንደ ኢትዮጵያ የመሰለች አገር ኢኮኖሚዋን ፋይናንስ ለማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ አስመልክቶ አማካሪ ሆነው ከተመረጡት ውስጥ ስሙን ለመጥቀስ የማልፈልገው አንዱ ኢኮኖሚስት ሃሳብ እንድለግሰው በኢሜይሌ ኮንታክት አድርጎኝ ነበር። እኔም ይህንን አስመልክቶ በሰፊው በመጽሃፌ ውስጥ “African Predicaments and the Method of Solving them Effectivelly“ እዚያ ውስጥ በስርዓት ስለተነተንኩ እሱን ገዝቶ ማንበብ እንደሚችል ብጠቁመው ያለኝ ነገር ከመጽሀፉ ውስጥ የሚፈልገውን ብቻ ኮፒ አድርጌ እንድልክለት ነበር። ይህ እንደማይቻል በማመልክት፣ ቀደም ብዬ በእንግሊዘኛ ያወጣዃቸውን ጽሁፎችን ብልክለት ሰውየው ወደ መሳደብ ነው ያመራው። ይህ ሰው ዓለም ባንክ ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ሰው ነው። ጆን ፐርኪን የሚባለው ቀድሞ የዓለም ባንክ ሲኒየር ኢኮኖሚስት የነበረና በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እየተከፈለው ይሰራ የነበረው ባንኩን ጥሎ ከወጣ በኋላ Economic Hitman”  ብሎ የጻፈው ዐይነት ሰው ነው። ባጭሩ የጠቅላይ ሚኒሰተራችን የኢኮኖሚ አማካሪዎች እንደነዚህ ዐይነት Economic Hitmen ብቻ ሳይሆኑ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተላላኪዎች ናቸው። በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ስልጣኔ እንዳይመጣ የሚታገሉ ናቸው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ኃይል እንዳይሆኑ መሰናክል የሚፈጥሩ ናቸው። የውስጥ ሀብት፣ የሰውም፣ ሆነ የተፈጥሮ በደንብ በመንቀሳቀስ ድህነት እየተወገደ ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚ (Sustainable Development) እንዲገነባ የሚያደርጉ አይደሉም። ዘለዓለማዊ ጥገኝነትና ድህነት የሚፈለፈልበትን ሁኔታ የሚያመቻቹ ናቸው። ይህ ዐይነቱ ሂደት በአገራችን ብቻ ሳይሆን ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባልዳበረበትና ዘራፊ መንግስታት(Predetarory States) በተስፋፉበት በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የሚታይ ሃቅ ነው።

ወደ ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህን ጋ ስንመጣ በመሰረቱ ተጠያቂው የክብር ዶ/ር ዲግሪ የሰጧት የአዲስ አበባና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። የምንጠይቃቸው በምን ዐይነት ቅድመ-ሁኔታ ወይም መመዘኛ ይህንን ዐይነቱን ክብር እንደለገሷት ቢነግሩን ደስ ይለናል። በሌላ ወገን አለማወቅ ከወንጀል ነፃ አያደርግም። ለማንኛውም አገራችን በዚህ ዐይነት ምሁራዊ እንቀቃሴና የተገለጸለት ኃይል ሊፈልቅበት በማይችለው ዩኒቨርሲት አማካይነት ሁለ-ገብ ዕድገትን ማየት በፍጹም አትችልም። በአገራችን የሚታየው ድህነት፣ የተዝረከረከና አቅድ የሌለው የከተማዎች አገነባብ፣ ሌሎች እሴትንና ባህልን የሚያዳክሙ ስራዎች በሙሉ ለመስፋፋት የቻሉት የትምህርት አስጣጡ ትችታዊ በሆነና ሁለ-ገብ በሆነ መልክ ለመዘጋጀት አለመቻሉ ነው። በተለይም አገራችን የውጭ ኤክስፐርት ነን ባዮች መጫወቻ የሆነችው ብቃትነት ያለውና ተቆርቋሪ የሆነ ምሁራዊ ኃይልና እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ነው። ባጭሩ ኃላፊነትና የሞራል ግዴታ የሚሰማው ምሁራዊ ኃይል በአገራችን ምድር ፈልጎ ማግኘት የሚቻልበት ሁነታ ያለ አይመስልም። በዚህ ዘርፍ በሚገባ እስካልተሰራና ድፍረት እስከሌለ ድረስ ሰለ አገር ማውራት በፍጹም አይቻልም

                                                              fekadubekele@gmx.de

                                                             

                                           https://www.youtube.com/watch?v=s513_tBeV-M

 

ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ከታች የሰፈሩትን መጻህፍት ተመልከቱ፣

David S.Landes; The Wealth and Poverty of Nations, London, 1999

David S Landes; The Unbounded Prometheus, Technological Change and Industrial

Development in Western Europe from 1750 to the Present, UK, 2003

Eric Dorn Brose; The Politics of Technological Change in Prussia: Out of the Shadow of

Antiquity, Princeton University Press, 1983

Erik S. Reinert; How Rich Countries Got Rich… and Why Poor Countries Stay Poor,

London, 2007

Frederick G.Lawrence , Patrik Beyne & Charles Hefling(eds.);  Macroeconomic Dynamics: An

Essay in Circulation Analysis, London, 1999

Frederick Soddy; Wealth, Virtual Wealth and Debt, London, 1983

Gary Herrigel; Industrial Constructions: The Sources of German Industrial Power, USA. 1996

James Angresano; The Political Economy of Gunnar Myrdal: An Institutional Basis for the

Transformation Problem, USA, 1997

Kate Raworth; Doughnut Economics; Seven Ways to Think Like a 21st-Century Economist,

London, 2017

Naomi Klein; The Shock Doctrine, London, 2007

Paul Mason; Post capitalism: A Guide to our Future, USA, 2015

Stephan Schulmeister; The Road to Prosperity, München, 20018