[gtranslate]

 

 

የግሎባላይዜሽን ውጤቱ -ያበጠው ሲፈነዳ፣ ህብረተሰቦች

ሲተረማመሱ! ለኛም ሲተርፈን !!

መግቢያ

በዘጠናዎቹ ዐመታት ግሎባላይዜሽን የሚባለው ጽንሰ-ሀሳብ በዜና ማሰራጫዎች ሲወራ፣ ለዓለም ማህበረ-ሰብ ጠቃሚነቱን ለማስረዳት የምዕራብ አገር ኤክስፐርቶች ወዲህና ወዲያ ውርውር ሲሉና የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ሊካተቱ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥድፊያ ሲደረግ፣ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አዲስ የቀን ብርሀንን የሚያይ መስሎት በጉጉት ይጠባበቅ ገባ። ከእንግዲህ ወዲያ ዓለም ወደ „መንደርነት“ እየተለወጠች ነው፤ እዚያ ውስጥ ገብቶ መወዳደርና ብቁነትንም ማሳየት ነው፤ በየቦታው የሚመረተውን ምርት ብቻ ሳይሆን ይህንንም ያሚያሽከረክረውን የፊናንስ ካፒታል ተካፋይ መሆንና በደስታ ዓለም ውስጥ እየተዝናኑ መኖር ነው የሚለው ብዙዎችን ወደ ማሳመን እንደገባ የማይታበል ሀቅ ነው። በመሆኑም ግሎባላይዜሽን አማራጭ የሌለው ነው፤ ይህንን ሀቅ አለመቀበልና በርን መዝጋት ለብዙ መቶ ዐመታት ተኝቶ እንደ መቅረት ይቆጠራል፤ ልናልፈው የማንችለው ታሪካዊ ግዴታ ነው ብለው የኒዎ ሊበራል ኢኮኖሚስቶችና የምዕራብ መንግስታት ለማሳመን የማያደርጉት ግፊትና የማያሰራጩት ዜና አልነበረም። ግሎባላይዜሽን ጥቂቱን የሚጠቅም ሌላውን ደግሞ የሚጎዳ (Zero-Sum game) ነው ብሎ ብዙ ሰዎችን ለማሳመን በጣም ከባድ ነበር። ስለዚህም ግሎባላይዜሽንን የሚቃወሙ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያዛባና ሀብት በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር እንዲውል የሚያደርግ ነው፤ አካባቢ እንዲቆሽሽ የሚያደርግና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል የሚያመጣ ነው ብለው ለማስተማር የሚጥሩትን እንደ ዕብድ የሚታዩበት፤ ግሎባላይዜሽንን መቃወም ማለት እንዳለ ካፒታሊዝምን መቃወምና እንደ መዋጋት የታመነበት ጊዜ ነበር። በግሎባላይዜሽን አራማጆች ዕምነት እነዚህን ተቃዋሚ ኃይሎች አጥብቆ መዋጋት እንደሚያስፈልግ የታመነበትና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ጊዜም ነበር።

ዛሬ በግልጽ እንደሚታየው ግሎባላይዜሽን እራሳቸውን ሰባኪዎችንንም እያስደነገጠ የመጣበት ወቅት ነው። ካለፈው ዐመት ከሰኔ 2007 ጀምሮ በአሜሪካን አገር በግልጽ እየታየ የመጣው በዕዳ የተገዙ ቤቶችና የአበዳሪ ባንኮች ቀውስ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዜጎች ቤት ገዛን፣ እፎይ ከእንግዲህ ወዲያ ተዝናንተን በቤታችን ውስጥ እንኖራለን ሲሉ ቀውሱ ሳይታስብ የዱብ ዕዳ ሆኖባቸው ቤታችን ነው ከሚሉት ውስጥ እየተፈናቀሉ በመውጣት በመኪኖቻቸው ውስጥ እንዲያድሩ መገደዳቸው፣ ግሎባላይዜሽን የተጠበቀውን ውጤት እንዳላመጣና እንደተወራለት ለሁሉም ደስታን እንዳላጎናጸፈ የዛሬው ተጨባጭ የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ያረጋግጣል። መኪኖቻቸውን ወደ ቤቶቻቸው የቀየሩና በየመንገዱ እንዲያድሩ የተገደዱ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ውሾችም ባለቤት አጥተው በየቦታው እንደሚንቀዋለሉ በየሬዲዮውና በየቴሌቪዥኑ የምንሰማውና የምናየው ነው። በአሜሪካን ፣ በካናዳና በሜክሲኮ መሀከል በተፈጸመው የነፃ ንግድ ስምምነት መሰረት የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ርካሽ የስራ ጉልበት ለማግኝት ሲሉ ኢንዱስትሪዎቻቸውን እየነቀሉ ወደ ካናዳና በተለይም ወደ ሜክሲኮ በመውሰዳቸው አሜሪካን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የስራ መስኮች እንደ ወደሙ የሚታወቅ ነው። ዐይን ተጨፍኖ የታመነበትና የተሰበከለት የነፃ ንግድ መፈክር ብዙ ህብረተሰብአዊ ቀውሶችን እያደረሰ ለመሆኑ ዜናዎችን ለሚከታተል፣ ኤንፎርሜሽኖችን ለሚሰበስብና ለሚመራመር ግልጽ እየሆነለት መጥቷል።

በተለይም በአሜሪካን የደረሰው በዕዳ የተሰሩ ቤቶች ቀውስ(subprime crisis)ጠቅላላውን የፊናንስ ገበያ( financial market) ማናጋት ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች (real economy) በመሸጋገር ከአሜሪካ አልፎ የዓለምን ኢኮኖሚ እንደሚያናጋው ብዙ ኤክስፐርቶች ይናገራሉ። ከአንድ ወር ጀምሮ የፊናንስ ገበያውን ረገብ ለማድረግ በአሜሪካን የሴንትራል ባንክ( federal reserve bank) የተወሰደውና የሚወሰደው ወለዱን ዝቅ ማድረግና ተጨማሪ ገንዘብ ለባንኮች መስጠት ስር የሰደደውን ችግር በፍጹም ሊፈታው እንደማይችል በዙ ኤክስፐርቶች ይናገራሉ። የአሁኑ የፊናንስ ገበያ ቀውስ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት እ.አ 1929 ዓ.ም ከተከሰተውና የዓለምን ንግድም ሆነ የምርት እንቅስቃሴ ካናጋው ጥልቀት ከነበረው የፊናንስ ቀውስ ሊተናነስ እንደማይችልና ብዙ የዓለም ማህበረሰቦችም የቀውሱ ሰለባ ለመሆን እንደሚችሉ ይነገራል። ይህ ማለት እኛንንም ይመለከተናል ማለት ነው። በሌላ በኩል ደገሞ ይህ ዐይነቱ ቀውስ የብዙ ሰዎች ዐይኖችንንም ሊከፍት እንደሚችል ግልጽ ነው። የዓለምን ኢኮኖሚ በአዲስ መልክ እንዲሚገመግሙና የህብረተሰብአቸውን አገነባብ ከዚህ እጅግ እልክና ሀብት አስጨራሽ ከሆነው ግሎባላይዜሽን ባሸገር እንደሚመለከቱና ትግላቸውን በአዲስ መልክ እንዲቀይሱ መንገድ እንደሚከፍት የሚወጡት በሳል ትንተናዎችና ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።

ከዚህ ስንነሳ እስዛሬ ድረስ በተለይም በኛ ዘንድ ሲያተራምሰን የቆየውንና ግራ ያጋባንን ግሎባላይዜሽን የሚለውን ጽንሰ-ሀሳብ እየተነተኑ መመልከቱ ለምንገነባት አዲስ ኢትዮጵያ መነሻ ሊሆነን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። በተለይም ዛሬ በአገራችን አፍጦ አግጦ የሚታየው ህዝባችንን የሚያራቁተውና የሚያተራምሰው የኢኮኖሚ ቀውስና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚደረገው ግፊትና ሜዳዎቻችንን ለአግሮ ነዳጅ የሚያገለግሉ አትክልቶችና ሰብሎች መትከያ ማድረግ ልንወጣው የማንችለው  ተጨማሪ ማጥ ውስጥ እንደሚከተን በማወቅ ካሁኑ ዝግጅት ማድረግ አለብን። ስለዚህም የግሎባላይዜሽንን ትርጉምና የሚያመጣውን ጠንቅ መረዳቱ ለምናደርገው ትግል ትንሽ ሊያግዝ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ። ይህንን በሚመለከት ሌሎችም ገንቢና ትምህርታዊ አስተያየታቸውን ቢሰጡ የአስተሳሰብ አድማሳችንን እንደሚያሰፋው ዕምነት አለኝ። ክርክራችንን እንቀጥል።

ግሎባላይዜሽን ማለት ምን ማለት ነው ?

ለብዙዎች፣ በተለይም የግሎባላይዜሽንን ጽንሰ-ሀሳብ ከውስጥና ሁለመንታዊ ጎኑን ሳይመረምሩ እንደ ጥሩ ነገርና ሊታለፍ የማይቻል ነገር አድርገው ሲወስዱ ሊገነዘቧችው የማይችሉ መዓት ቁም ነገሮች አሉ። በተለይም የኔዎ ለበራል ኤኮኖሚስቶችና የምዕራብ መንግስታት የሚወረውሩትን በቀላሉ እንደ ዕውነት የሚወሰዱ አነጋገሮችና ትንተናዎች የጽንሰ-ሀሳቡን ትርጉምነተና ተግባራዊነት ጭንቅላታቸውን አስጨንቀው ሊያወጡና ሊያወርዱ ለማይፈልጉ ግለሰቦችም ሆነ በቡድን ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ግሎባላይዜሽን አዎንታዊ ውጤት ብቻ ያለው እንጂ፣ በፍጹም ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልን እንደማያመጣ ነው። በተጨማሪም አንድ አገር የግሎባላይዜሽን ተዋናዮች መዳፍ ስር በምትወድቅበት ጊዜ በዚያ ህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰተው ኢኮኖሚያዊ መዛነፍ (economic injustice) ፣ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ለውጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቆላለፍ ሊያመጣ የሚችለው የብሄራዊ-ነፃነት ገፈፋና ውስጣዊ ጭቆና፣ እንዲሁም ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልና የአካባቢ ቀውስ ለብዙዎቹ የነዚህን ኤክስፐርት ነን ባዮችን አገላለጽ አፋቸውን ከፍተው ለሚያዳምጡ አይታያቸውም። ህብረተሰብአዊና የታሪክ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ለአንድ አፍታ ቆም በማለት መሰረተ ሀሳቡ ወደ ተግባር በሚመነዘርበት ጊዜ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ አያወጡም አያወርዱም። በሌላ ወገን ደግሞ በግሎባላይዜሽንም ሆነ በሌላ ስም የሚካሄድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊነት አጥፊም ሆነ ገንቢ ጎን እንዳለው ለዚህ ጸሀፊ ግልጽ ነው። ይህ ጸሀፊ ግሎባላይዜሽንን በደፈናው የሚጠላ ሳይሆን ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በመገምገም ውስጣዊ-ኃይልን በማጠንከር ጠቃሚና ለህብረተሰብ ግንባታ ሊያገለግሉ የሚችሉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረተ-ሃሳቦችን በመውሰድ የተረጋጋ ህብረተሰብ እንዲመሰረት ከበፊቱ ዝግጅት ማደረግ እንደሚያስፈልግ ያምናል። በተለይም የምሁር እንቅስቃሴ ደካማ በሆነበትና አንድ አመለካከት ሰፍኖ ሌላ ሂሳዊ አመለካከት እንደ ሰይጣን በሚታይበት እንደኛ ባለ ህብረተሰብ ውስጥና ውጭ አገር በሚገኘው አብዛኛው የኢትየጵያዊ ኮሙኒቲ ዛሬ እንደምናየው ግሎባላይዜሽን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንሚያመዝን መታወቅ አለበት።

ወደ ትርጉሙም ስንመጣ፣ አብዛኛውን ጊዜ ግሎባላይዜሽን በንጹህ ኢኮኖሚ መልኩ ብቻ ነው የሚወሰደው። ይህም ቢሆን እንኳ በተሟላ መልኩ አይገመገምም። ለብዞዎቻችን ግሎባላይዜሽን ማለት ተራ የምርት ክንውን የሚካሄድበት ኢኮኖሚያዊ ሂደት ሲሆን፣ ለብዙ ሰዎች የስራ መስክ የሚከፍትና ገቢ የሚያሰገኝላቸውና በዚህም ተደስተው እንደሚኖሩ  ነው ተራ ግንዛቤ ውስጥ የሚገባው። በግሎባለይዜሽን አማካይነት የሚከፈተው የስራ መስክ በቂ የቀንም ሆነ የወር አበል ያስገኝ አያስገኝ፣ በዚያውም የሰራተኛው የመግዛት ኃይል (buying power) ይጨመር አይጨመር፣ ለመንግስት የሚያመጣው በቀረጥ በኩል ተጨማሪ ገቢ ይኑር አይኑር፣ በተለይም ደግሞ በጠቅላለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ(macro economic performance) ላይ ሊኖረው የሚችለው ሚና፣ በግሎባላይዜሽን ስም የሚተከሉት ፋብሪካዎችና ወይም የሚካሄዱት የእርሻ ተግባሮች ከባንኮችና ከሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ጋር ሊኖራቸው የሚችለው ትስስርና በዚህም አማካይነት የሚገኘው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ውጤት ምርምር ውስጥ አይገባም። ዋናው ቁም ነገር ከግሎባላይዜሽን ልናመልጥ ስለማንችል ገብተን እንደፋደፍ ነው። በተለይም ከሀበሻ ይልቅ ከፈረንጅ አፍ የሚወረወር ሁሉ ወርቅ ቃል የሚመስላቸውና በነሱም የሚጻፈው ጽሁፍ ካለብዙ ውጣ ውረድ እንደ ዕውነት ተወስዶ በሚታመንበት የፖለቲካ እንቅስቃሴና ህብረተሰብ ውስጥ ብዙዎችን ለማሳመን ያለው ችግር በጣም ከባድ ነው።

ግሎባላይዜሽን ማለት በአጭሩ ዓለም አቀፋዊ የምርት ክንውን፣ የንግድና የፊናንስ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ጽንሰ-ሀሳቡ ጎልቶ የመጣው በ90ዎቹ ዓ.ም ነው። ከዚያ በፊት ግን የምርት ክንዋኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ አይካሄድም ማለት አይደለም። ግሎባላይዜሽን ቢያንስ የአራት መቶ ዐመት ዕድሜ እንዳለው፣ዕድገቱም ከአውሮፓ የህብረ-ብሄር(Nation-State) አመሰራረትና ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በጥብቅ እንደተያያዘና ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ በተለይም ጥሬ ሀብትን ለመቀራመት የግዴታ ወደ ውጭ መስፋፋት ስላስፈለገ በዚህም ምክንያት ቀስ በቀስ በተለይም የንግድ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እየያዘ እንደመጣ  ከኒዎ ሊበራሊዝም የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው የኢኮኖሚ ሳይንስ አዋቂዎችና የኢኮኖሚ ታሪክ ተመራማሪዎች በሰፊውና በሚመረቃ መልክ ያስረዳሉ። ያም ሆነ ይህ ታሪካዊ አመጣጡን ትተን ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዐመታት የተካሄደውን ዓለም አቀፋዊ የምርትና የንግድ እንቅስቃሴ ስንመለከት መቶና ከሁለት መቶ ዐመት በፊት ከነበረው ሁኔታ በዐይነትም ሆነ በብዛት ከፍተኛ ዕድገትን እንዳሳየ ካለብዙ ምርምር መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ምርትና ንግድ እንዲሁም የፊናንስ እንቅስቃሴዎች ጥልቀትንና ስፋትን እያገኙ በመምጣት የዓለምን ህዝብ ዕድል ወሳኝ ለመሆን በቅተዋል። ዓለም አቀፋዊ የህዝብ እንቅስቃሴም(social mobility) ከመቼውም ጊዜ እየጨመረ በመምጣት ህብረተሰብአዊ „ውህደትና“  መመሰቃቀሎች እየታዩ ነው። በዚህም ምክንያት አገር ውስጥ የስራ ዕድል ያላገኘ ሌላ አገር በመሄድ ተቀጥሮ በመስራት የሌላ „ህብረተሰብ አካል“ በመሆን ህይወቱና ዕድሉ ተወልዶ ባደገበት አገር ሳይሆን በሌላ አገር እንዲወሰን የሆነው ህዝብ ቁጥር ጥቂት አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ የምርት ክንውን ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ ፣ የአንድ የመጨረሻ ምርት ውጤት የተለያዩ ክፍሎች በተለያዩ አገሮች በመመረትና በዋናው አምራች አገር ውስጥ በመገጣጠም ብዙም ሳያወጣ ሳያወርድ ገዝቶ ለሚጠቀመው ህዝብ ለምሳሌ፣ የማርሴዲስ መኪና በጀርመን ብቻ ተመርቶ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ የሚመስላቸው ጥቂት እንዳይደሉ መገመት ይቻላል። በሌላ አነጋገር ከስራ ጉልበት ዋጋ አንጻርም ሆነ በአካባቢው የጥሬ ሀብት ማግኘት አንፃር የማርሴዲስ መኪና የተለያዩ ክፍሎች በተለያዩ አገሮች በመመረት የተለያዩ አገር ሰዎች የስራ ውጤት(value-added) ሊሆን የበቃበት ወቅት ነው። እንደዚሁም የምርት ዋጋን በተቻለ መጠን ከመቀነስ አንፃር፣ የስራ ጉልበትንና የመገናኛን፣ እንዲሁም የገበያንና የደንበኞችን አስፈላጊነት ግምት ውስጥ በማስገባት አንድን ፋብሪካ እንዳለ ወይም ደግሞ የተወሰነውን ብቻ ሌላ ቦታ በመውሰድና በመትከል ገበያን ለመቆጣጠር የሚካሄደው ዓለም አቀፋዊ ውድድር ግሎባላይዜሽን ይባላል። አንድ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያ የምርቱን እንቅስቃሴ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው ጥረት ሲያደርግ ዋናው ዐላማው በተቻለ መጠን የማምረቻን ዋጋ(production cost) ለመቀነስና ከፍተኛ ትርፍን ለማትረፍና በአሸናፊነት ወጥቶ የገበያውን ከፍተኛ ክፍል በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ እንጂ ፋብሪካውን የሚተክልበትን አገር ዕድገት መልክ ለመስጠትና ታሪካዊ አስተዋፅፆ ለማደረግ አይደለም። በተጨማሪም የሰራተኞች ህወይት ይጠበቅ አይጠበቅ፣ የተወሰኑ የአካባቢን ስንታንደርድ ያሟላ አያሟላ ጉዳዩ አይደለም። በዚህም ምክንያት ከሶስተኛው ዓለም አገሮች አንፃር ብዙም ሳይታሰብባቸው በየአገሮች የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች በሰው ላይ ጉዳትን እንዳስከተሉና ለአካባቢም መቆሸሽና ለረጅም ገዜ ጤንነት ቀውስ ጠንቅ በመሆን አገሮች ሊወጡ የማይችሉበት ማጥ ውስጥ እንደወደቁ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በተለይም ደግሞ የአካባቢን ንጽህና ለመጠበቅና ለመንከባከብ ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኝበት አገር ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች እዚያ ሄደው ለማምረት ይቀላቸዋል። ባለስልጣናትንም በማባለግ በአጥፊነት ባህርያቸው ይገፉበታል። ይህንን የአካባቢ ቀውስ(externalities) ለማስወገድና አዲስ ህይወት ለመመስረት ብዙ ዐመታት እንደሚፈጅ መገመት ይቻላል። ይህም ደግሞ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው በአካባቢ ቀውስ የተጠቃችው አገር አንድ ቀን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የበቃች እንደሆን ብቻ ነው።

ከዘጠናኛው ዓ.ም መጀምሪያ ጎልቶ የመጣውና ብዙ የተወራለት ግሎባላይዜሽን ከጥንታዊው ባህርዩ የሚለይባቸው አንዳንድ መሰረተ ጉዳዮች አሉ። የምርት ክንውን ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዳለ ሆኖ፣ በተለይም ከሰማኒያኛው ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በጉልህ እየታየ የመጣው በትላልቅ ኩባንያዎች ዘንድ የጦፈ ውድድር ላቅ ብለው የሚገኙ ኩባንያዎች ደካሞችን እንዲውጡ ወይም ደግሞ የካምፓኒውን ከፍተኛ ድርሻ በመቀራመት በማኔጂሜንትና በምርት ክንውን ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ሊመጡ ቻሉ። አንዱ ኩባንያ ተመሳሳይ ምርት ያሚያመርትን ሌላ ኩባንያን መዋጥና አንድ ላይ መዋሃድ(acquisition and merging) ፣ የአንድን ኩባንያ የተወሰነ ክፍል ወደ ሌላ አገር በመውሰድና ራሱ ብቻውን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ማድረግና ትርፍ አካባች መሆን፣ እነዚህን የመሳሰሉት ከጥንቱ የግሎባላይዜሽን ዐይነት የሚለዩ ሂደቶች ናቸው። አንድ የሌላ አገር ኩባንያ ተመሳሳይ ምርት ከሚያመርት ሌላ አገር ኩባንያ ጋር በሚዋሃድበት ጊዜ ትርፋማ ያልሆነውን የአንዱን ኩባንያ ክፍል እንዲፈርስ ይደረጋል። የበላይነትን የተቀዳጀው ኩባንያ ትርፋማ ነው ብሎ በሚገምተው ክፍል(segment) ላይ ብቻ በማትኮር በተቻለ መጠን የዋጋ ቅነሳ ሰትራቴጂ ይከተላል። በቅናሽ የመለዋወጫ ዕቃዎችና የጥሬ ሀብት ሊገዛ የሚችልበትንና አነስ ባለ የሰው ጉልበት በብዛት አምርቶ ከፍተኛ ትርፍ ሊያገኝ የሚችልበትን ስልት ያወጣል ማለት ነው። ስለሆነም በተዋጠው ኩባንያው ውስጥ ብዙ ዐመታት የሰሩ ሰራተኞች የዚህ አዲስ የኩባንያዎች መዋሃድና ትርፍ ማካበት ስትራቴጂ ሰለባ ይሆናሉ ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ከፊናንስ ገበያ ላይ አዳዲስ ኢንቬስተሮች ለማግኘት የተቆላለፈው ኩባንያ የኢንቬስተሮችን ድርሻ(share holder value)ከፍ ለማድረግ ሲል በየጊዜው የምርት ዋጋ(production cost) ቅነሳ ስትራቴጂ እንዲከተል ይገደዳል ማለት ነው። እንደዚህ ሲያደርግ ብቻና ትርፉ በየጊዜው እያደገ ሲሄድ የድርሻው ዋጋ (stock market value) ከፍ 㗹እያለ ይሄዳል ማለት ነው። በአዲሱ የግሎባላይዜሽን እንቅስቃሴ ፍልስፍና መሰረት ወሳኙ የሰራተኞች የስራ ሁኔታና ገቢ ማደግ ሳይሆን የኢንቬስተሮች ድርሻ(share holder value) ማደግና 㜎ይህንንም ለሟሟላትና በልጦ መገኘት ከፍተኛ ቦታን ይይዛሉ ማለት ነው። በዚህ መልክ በተለይም ባለፉት አስራሰባት ዐመታት አንድ ኢንዱስትሪ ተነቅሎ ወደ ሌላ ቦታ ተወስዶ ሲተከል የስራ ቦታውን ያጣ፣ በዚህም ምክንያት ከድሮው የተሻለ የኑሮ ሁኔታው ዝቅ ብሎ እንዲኖርና የስራ አጥ በመሆን ገበያውን ያጥለቀለቀው፣ ቀስ እያልኩ እክፍላለሁ ብሎ ከባንክ ተበድሮ ቤት የሰራና ለመክፈል ባለመቻሉ ንብረቴ ነው ብሎ ከገመተው የተፈናቀለውና ትዳሩን ያፈረሰው፣ በዚህም ምክንያት ህሊናዊ ቀውስ ደርሶበት የተጎሳቆለው በብዙ ሚለዮን የሚቆጠር ሰራተኛ ነው። በአዲስ የማኔጂሜንት ፍልስፍና የሰለጠነው፣ በቅድሚያ ምርትን ሳይሆን ትርፍን የሚያሰላው አዲሱ የማኔጀር የህብረተሰብ ክፍል(managerial class) በዚህ ዐይነት ጭፍን አመለካከቱ ህበረተሰብአዊ ቀውስ አድርሷል። የዛሬው የካፒታሊስት ሰርዓት የስድሳኛውና የሰባኛው ዓ.ም ዐይነት አይደለም። በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማበጥና ከባንኮች ጋር መቆላለፍ የየአገሩ መንግስታት ከነበራቸው ህዝባዊ ሚና በመገፍተር የሰፊውን ህዝብ መብት እንዲነጠቅ በማድረግ ድሮ በሙያ ማህበሩ㜎ተጠሪዎቹ አማካይነት መብቱን ያሰጠብቅ የነበረው ሰራተኛ ካለፈው ሃያ ዐመት ጋር ሲወዳደር ዛሬ አቅመቢስ ሆኗል። በዚህ ላይ ደግሞ እንደ አውሮፓ አንድነት ገበያ ዐይነቱ እየተቆላለፈ በመምጣቱ የተነሳ ሰራተኞች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በመሄድ በቅናሽ ደሞዝ የሚሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ የቀደሞው ዐይነት(Manchester Capitalism) ሰራተኞችን የመበዝበዙና መብታቸውን የመንጠቁ ሁኔታ ከምንጊዜውም እያየለ መጥቷል።

በተለይም ባለፉት 17 ዓመታት በኢንዱስትሪዎች፣ በመገናኛ መስኮችና በባንኮች መሀከል የተካሄደውን መዋዋጥ፣ ውህደትና መተሳሰር ስንመለከት የተወራለት ግሎባላይዜሽን ለብዙ ቢሊዮን ካፒታል ውድመት ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ በዳይምለር ቤንዝና(ማርሴዲስ) በክራይስለር መሀከል የተፈጸመው ውህደት ከአምስት ዓመት በኋላ የተጠበቀውን ውጤት ስላላመጣ በብዙ ቢለዮን ኦይሮ ኪሳራ ተሸጧል። እንደዚሁም ዲኤም ደብልዩ ከሮቨር ጋር ያደረገውን ውህደት አፍርሶ ወደ ቀድሞው ቦታ በመመለስ ትርፋማ ሆኗል። እንደ ስልክ የመሳሰሉ ካምፓኒዎች ደግሞ ሌላ ተመሳሳይ ካምፓኒ ለመዋጥ ከባንኮች ብዙ ቢሊዮን ኦይሮ በመበደራቸው በዕዳ ዘፍቀው ይገኛሉ። ከቴክኖሎጂ መሻሻል በስተቀር ለሰራተኛውም ሆነ ለተጠቃሚው ያመጣው ይህን ያህልም የሚጠቅም አይደለም። በአጭሩ በዚህ መልክ የተካሄደው መበላላትና መቆላለፍ ብዙ ሀብት እንዲወድምና ሰራተኛው እንዲበደልና ከስራው መስኩ እንዲባረር አድርጓል።

ከላይ እንደተጠቀሰው የምርት ክንውን ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሲይዝ የምርት ማምረቻን ዋጋና(production cost) ከፍተኛ ትርፍን ለማካበት ስሌት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ በአጭሩ ተቀምጧል። በብዙ የኒዎ ሊበራል ኢኮኖሚስቶችና በየመንግስቶቻቸው እንደሚሰበከው የምርት ክንዋኔ ዓለም አቀፍ ባህርይ መያዝ ለአንድ አገር ጤናማና የተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያመጣላት አይችልም። ጠቅላላውን ኢኮኖሚ(Macro Economy)ትተን በግሎባላይዜሽን ስም አንድ ኢንዱስትሪ አንድ የሶስተኛው ዓለም አገር ሲተከል ማምጣት ያለበትን አዎንታዊ ውጤት ጠጋ ብለን እንመልከት። በመስረቱ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ተከላ መቶ በመቶ በባለቤቱ ሀብት(capital) ብቻ ሊንቀሳቀስ የሚችል አይደለም። ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ በቤተሰብ ቁጥጥር ስር ያለ ኢንዱስትሪ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ከመጠነኛ ኢንዱስትሪ አንስቶ እስከትልቅ ድረስ ለመንቀሳቀሳ በደንቡ መሰረት ከባንክ ተጨማሪ ብድር መበደር አለበት። በስምምነቱ መሰረት የኢንዱስትሪው ባለቤት ለባንኩ ወለድና የተወሰነውን የካፒታል ክፍል በየጊዜው ማስተላለፍ አለበት። በባንኩና በኢንዱስትሪው መስክ መሀከል መደጋገፍና ጥገኝነት አለ ማለት ነው። የባንኩ መስክ ሊዳብርና ሊስፋፋ የሚችለው ብድር ሲያበድርና ወለድ ሲቀበል ብቻ ነው። ሶስተኛው ዓለም ሄደው የሚተከሉ ኢንዱስትሪዎችን ስንመለከት ግን ከየአገሩ ባንክ ጋር ምንም ግኑኝነት የላቸውም። ለካፒታል የሚተማመኑት ላይ ሆኖ ከሚቆጣጠራቸው ከእናታቸው ኩባንያ ነው። እንደዚህ ዐይነት ግኑኝነት አለመፈጠር በሶስተኛው ዓለም አገር ውስጥ በምርት ክንውን ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ኢኮኖሚ እንዳይስፋፋ ከማገዱም በላይ የአገር ውስጥ ባንኮች ባለው የተገደበ የገንዘብ እንቅስቃሴሰ ሊያበድሩ የሚችሉትን በቂ ካፒታል ሊያገኙ አይችሉም። ከዚህ ወጣ ስንል በአገር ውስጥ የሚመረትን ጥሬ ሀብት በሚመለከት፣ ወይም የመለዋወጫ ዕቃዎችን ብንወስድ አዲስ የሚተከለው ኢንዱስትሪ ከእናት ኢንዱስትሪው በሚመጣለት የጥሬ ሀብትና የመለዋወጫ ዕቃ ላይ ነው የሚተማመነው እንጂ አዚያው አገር ውስጥ እየገዛ የምርቱን ክንዋኔ የሚያካሂድ አይደለም ማለት ነው። በዚህም ማን እንደሚያመርት፣ ለማን እንደሚመረትና ምን እንደሚመረት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እናት ኢንዱስትሪው ወሳኝ ሚናን ይጫወታል ማለት ነው። አዲስ በተተከለው ኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችንም የወር ገቢ ስንመለከት፣ ገቢያቸው እራሳቸው ያመረቱትን የፍጆታ ዕቃ እንኳ ገዝተው ሊጠቀሙ የሚያሰችላቸው አይደለም። ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሰራተኛው በሚያገኘው ገቢ ገዝቶ ሊጠቀም የሚችለው ኢንፎርማል ሴክተር ተብለው በሚታወቁና ከአዲሱ ኢንዱስትሪ ጋር ምንም ዐይነት ውስጣዊ ግኑኝነት(organic link) ከሌላቸው መስኮች እየገዛ ነው። በሌላ አነጋገር አዲስ የሚተከለው ኢንዱስትሪ ለአንድ አገር የውስጥ ገበያ(home market) ማደግና የስራ ክፍፍል( division of labour)መዳበር የሚያመጣው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህ መልክ ከንጹህ የምርት ማምረቻ ዋጋ ቅነሳና ትርፍ ማካበት አንጻር የተሰላው የኢንዱስትሪ ተከላ ለከተማ ዕድገት፣ ለባህል መስፋፋት፣ ለፈጠራ ስራ ማበብና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር፣ ባጭሩ ለጠቅላላው ኢኮኖሚ ዕድገትና ህብረተሰቡ በተለያዩ ድሮች እንዲተሳሰር ለማድረግ ያለው አስተዋፅዖ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ደግሞ አንድ አገር እንደ አገር ሊያድግና ሊጠነክር የሚችለው ከሁሉም አንፃር የስራ ክፍፍል ሲዳብርና ይህ እንዲሻሻል ህብረተሰቡ አዲስ የስራ ባህል ሲማር ብቻ ነው። በግሎባላይዜሽን ስም የተስፋፋው ዓለም አቀፋዊ የምርት ክንዋኔ ከላይ የተጠቀሰውን ህብረተሰብአዊ ዕድገት ከማምጣት ይልቅ ሰራተኛውን ንጹህ የዋጋ አካል(cost factor) አድርጎ በመቁጠር ሰራተኛው የባሪያ ደሞዝ እየተከፈለው ከዓመት ዓመት የኑሮው ሁኔታ እንዳይሻሻል ያደርጋል። ልጆችና የልጅ ልጆቹም የዚህ በግሎባላይዜሽን ስም የሚካሄድ አዲሰ የብዝበዛ ሰለባ በመሆን ዘላለማቸውን ዕውነተኛ ነጻነታቸውን ተነፍገው ቀጭጨው እንዲቀሩ ይገደዳሉ።

ከዚህ ወጣ ስንል ደግሞ በዚህ ዐይነት መልክ የሚካሄደው ግሎባላይዜሽን በሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም የፖለቲካ ንቃተ ህሊናና ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴዎች ጎልተው በማይታዩባቸው አገሮች የሚያመጣው ውጤት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ ሄዷል። በዚህ መልክ በተለይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የውሃ አከፋፋይ መስክን፣ የመብራትና የቴሌኮሙኒኬሽንን መስኮችን መግዛት የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ስትራቴጂ ሆኗል። እነዚህ በየአገሩ ሰተት ብለው የገቡ ትላልቅ ኩባንያዎች የየመንግስታቱን ደካማ የመከራከር ጎንና ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና ዝቅተኛነት በመጠቀም ኢንቬስት ከማድረግ ይልቅ ትርፋማ በሚሏቸው ክፍሎች(segments) ላይ ብቻ በማትኮር አብዛኛውን የስራ መስክ በመዝጋት ትርፍ ያካብታሉ። ለምሳሌ ለሰፊው ህዝብ ሊዳረስ የሚችል ቋሚ ስልክ (fixed telefon line) ከመትከል ይልቅ የተወሰነውን ክፍል በማውደም ተንቀሳቃሽ ስልክ(mobile) ያስፋፋሉ ። በዚህ መልክ አንድ አገር አዲስ ቴክኖሎጂ ለመማርና በሰፊው የስልክ መስመር ለመዘርጋት ያላት ዕድል ይዘጋል ማለት ነው። የመብራትና የውሃም ጉዳይ እንደዚሁ ሲሆን፣ በተለይም ውሃን በሚመለከት ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች ለሰፊው ተጠቃሚ ህዝብ አዳዲስ ቧንቧዎች በመዘርጋት ንጹህ ውሃ እንዲጠጣ ዕድል አይሰጡትም። ለምሳሌ የፈረንሳይና አንድ የአሜሪካን የውሃ ካምፓኒ የፊልፕንን የውሃ ኩባንያ ከገዙ በኋላ ለተጠቃሚው ህዝብ ንጹህ ውሃ ለማዳረስ ፈቃደኛ አልሆኑም ። በዚህም ምክንያት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቆሻሻ ውሃ እንዲጠጣ ተገዷል። በሙስና የዘፈቀውም መንግስት ቆሻሻ ውሃ ለሚጠጣው ህዝብ ሊደርስለት አልቻለም። በዚህም ምክንያት የአንዳንድ አገሮች መንግስታት ለትላልቅ ኩባንያዎች የሸጡትን የህዝብ ንብረት እንደገና በኪሳራ መልሰው እንዲገዙ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥፘል።

ከላይ የተዘረዘረውን የግሎባላይዜሽን ሂደት በአጠቃላይ ስንመለከት በተለይም በዚህ ዓለም አቀፋዊ የምርት ክንዋኔ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የወስጥ ገበያ በፍጹም ሊያድግና ከውስጥ ህብረተሰብአዊ መተሳሰር ሊፈጠር አልቻለም። የስራ ክፍፍል ሊዳብርና ሊስፋፋ በማይችልበት ሁኔታ ውሰጥ ዕውነተኛ ግለሰብአዊ ፈጠራና ድርጊት አይዳብርም። ይህ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊታይና የሳይንስ ዕድገት  በፍጹም ሊኖር አይችልም። የቴክኖሎጂ ዕድገት በማይታይበትና ህብረተሰብአዊ የስራ ክፍፍል በማይዳብርበት ቦታ አንድ አገር እንደ ህብረተሰብ ልትገነባና ለህዝቦቿ የኑሮ መረጋገጫ ሊሆኑ የሚችሉ መሰረታዊ ነገሮችን ልታቀርብ አትችልም። ግለሰቦችም ሆነ ጠቅላላው ህብረተሰብ ነጻነት ተሰምቷቸው ማንነታቸውን በማወቅ ታሪክን እየሰሩ ብሄራዊ ነፃነታቸውን ሊያስከብሩ አይችሉም። በአጭሩ ግሎባላይዜሽን ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ ነገሮች ሊያሟላ የማይችል ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቦች እንዲመሰቃቀሉና እርስ በርስ እንዲበላሉ በር የከፈተና የሚከፍት ነው። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናየው ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል፣ የሀብት መዛነፍና የማያስፈልግ የርስ በርስ ጦርነትና የታሪክና የባህል ወድመት፣ እንዲሁም ደግሞ በወጣት ልጆች ላይ የሚደርሰው እጅግ የሚዘገንን ስራ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዚህ እጅግ በፈጠነ መልክ በየአገሮች ውስጥ እየሰገሰገ ከገባና ታሪካዊ ሂደቶችን ካላገናዘበ የግሎባላይዜሸን ሂደት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ ግሎባላይዜሽንን እንደ ዕድገት አምጭና አጋዥ አድርገን ልንቆጥር አንችልም። ብዙ ጥናቶችና ያለው ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው።

ከምርት ዓለም አቀፋዊነት ወደ ፊናንስ ገበያ !

ግሎባላይዜሽን በምርት ክንውን ዓለም አቀፋዊነትና „በዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍል“ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ለኢንዱስትሪ ተከላም ሆነ ምርት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው ከተፈለገ የፊናንስ ገበያ መዳበር እጅግ አስፈላጊ ነው። ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ባለው የውጭ ገንዘብ ብቻ ነው ምርት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተወስዶ ሊሸጥና ኢንዱስትሪዎችም ባህርን አቋርጠው ሊተከሉ የሚችሉት። በዚህ ረገድ ለግሎባላይዜሽን መስፋፋት የግዴታ በተለያየ መልከ ሊገለጽ የሚችል የገንዘብ ገበያ መዳበር አስፈላጊ ነው።

በተለይም እ.አ ከ1973/74 ዓ.ም በኋላ የተከሰተው ልዩ የኢኮኖሚ ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ የፊናንስ ገበያ እንዲያድግና ራሱን ችሎ እንዲወጣ መንገዱን አዘጋጅቶለታል። በዚሁ ዓ.ም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በጥልቀትም ሆነ በስፋት ስር እየሰደደ የመጣው በኢንዱስትሪ አገሮች የታየው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለፊናንስ ገበያ ማደግ የራሱን አስተዋጽዖ ሊያደርግ ችሏል። በስራ ላይ ሊውል ያልቻለው ካፒታል(ገንዘብ) ትርፍ ወደ ሚያመጣበት ቦታ በመሸጋሸግ ብድር ለሚፈልጉ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በተለይም በኢንዱስትሪ እያደጉ በመጡ እንደ እነ ሜክሲኮና ብራዚል እንዲሁም ደቡብ ኮርያ ለመሳሰሉ አገሮች የካፒታል ምንጭ ሆኗል። ይህንን ጉዳይ የተገነዘቡ ገንዘባችውን በምርት ክንውን ላይ ለማዋል ያልቻሉ ባለሀብታሞች በተለይም እንደ ለንደን የመሳሰለው ከተማ ባንኮች ውስጥ በማሰቀመጥ የኦይሮ ዶላር ገበያ(Euro-Dollar Market) ተብሎ ለሚጠራው ልዩ የፊናንስ ገበያ መቋቋምና ማደግ አመቺ ሁኔታ ፈጥረዋል። በተለይም ትላልቅ የአሜሪካን ባንኮች የተትረፈረፈውን የዶላር ክምችታቸውን ወደ ለንደን በማዘዋወር ከፍተኛ ወለድ የሚያካብቱበት ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ችሏል። በተጨማሪም በዘይት ዋጋ መወደድ ምክንያት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ያካበቱ የዘይት አምራች አገሮች በየአገሮቻቸው ኢንቬስት ሊያደርጉ ያልቻሉትን ዶላር በለንደንና በአንዳንድ ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ትናንሽ አገሮች በማስቀመጥ (recycle) ለዓለም አቀፋዊ የዕዳ ማደግና መስፋፋት ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል። በተለይም አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮና አንዳንድ ትንሽ 㗹ዕድገት የሚታይባቸው አገሮች ከካፒታል ገበያ ላይ ዶላር በመበደር ኢንዱስትሪዎችን በየአገሮቻቸው በመትከል ትክክለኛ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለመከተል የቻሉ መስሎ ታያቸው። ይህ ከካፒታል ገበያ ላይ ዶላርን እየተበደሩ መውሰድና ኢንዱስትሪዎችን መትከል በአንድ በኩል በየአገሮች ውስጥ ያልተስተካከለና አካባቢን የሚያቆሽሽ ዕድገት ሲያመጣ ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ለኢንዱስትሪ አገሮች አዲስ ገበያን ፈጠረላቸው። ምክንያቱም በተበደሩት ዶላር የግዴታ ማሽኖችንና 㜎የመለዋወጫ ዕቃዎችን ከኢንዱስትሪ አገሮች መግዛት ስላለባቸው ነው። ይህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሁለት ሁኔታዎችን ፈጠረ። እነዚህ ተበዳሪ አገሮች ገበያ በመሆን ዶላሩን መልሰው ወደ ኢንደስትሪ አገር ባንኮች ማስተላለፍ ነበረባቸው። በተጨማሪም ወለድና የወለድ ወለድ(compound interest)በመክፈል ከተበላሸ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ጋር ተደምሮ የዕዳው መጠን እየተቆለለና ሊከፍሉ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ መጣ። በተለይም የፕሬዚደንት ሬገን አስተዳደር የተከተለው ወለዱን ከፍ የሚያደርግ ፖሊሲ- በጊዜው ወለዱ 20% ያህል አድጎ ነበር- እንደ ሜክሲኮ የመሳሰሉ አገሮችን ብድሩን በተባለው ወቅት መክፈል የማይችሉበት ሁኔታ ፈጠረ። ይህ የብድር ቀውስ እ.አ በ1982 ዓ.ም ላይ አፍጦ አግጦ በመውጣት በተለይም የአሜረካንን ባንኮች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከተታቸው። እነ አይ ኤም ኤፍ የመሳሰሉት በመፘፘጥ ሜክሲኮ የተወሰነውን ዕዳ ልትከፍል የምትችልበትን ሁኔታ አዘጋጁ። ለዚህ ደግሞ ሜክሲኮ ለባንኮች ዕዳውን ለመክፈል እንደገና በአይ ኤምኤፍ አማካይነት ሌላ ብድር ማግኘት ነበረባት። በዚህ ዕዳውን እዚያው በዚያው ማሸጋሸግ(debt reschduling) ባንኮች ለጊዜው እስትንፋስ ሲያገኙ የሚክሲኮና የሌሎች ተበዳሪ አገሮች ዕዳ እየተቆለለና ወደ ውስጥ የሚፈልጉትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግና ለህዝቦቻቸው የኑሮ ማረጋገጫ የሆነ የስራ መስክ ሊከፍቱ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። በተለይም ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ የአይ ኤምኤፍ ሚና እያደገ መምጣትና በነዚህ አገሮች ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ጣልቃ መግባት ያለውን የተቆጠበ ሀብት(scarce resources) በስነ-ስርዓት ተግባር ላይ በማዋል ከውስጥ ዕውነተኛ ሀብት(real wealth) እንዳይዳብርና ህዝቦቻቸውም ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አገደ። የነዚህ አገሮች ደራሽ ከበርቴዎችና የመንግስት ቢሮክራቶች ከፊናንስ ገበያ ጋር በመቆላለፍ ያልተስተካከለ ዕድገትን በማራማድ በዚያውም መጠን በከፍተኛ ደረጃ ህብረተሰብአዊ ጭቆናን አስፋፉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በነዚህ አገሮች ውስጥ የተፈጥሮ የማሰብ ኃይልን በማናጋት የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ወደ አመጽና ወደ አልባሌ ቦታዎች በማሰማራት አጠቃላይና የተወሳሰበ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ፈጠረ። እንደ ሜክሲኮና ብራዚል የመሳሰሉት አገሮች ውስጥ በተለይም በድረግ(Drug) የናጠጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመፈጠር ለአገዛዙ በቀላሉ መፈናፈኛ እንዳይኖረው አገዱ። በተለይም ዛሬ ሜክሲኮ በድረግ ካርቴሎች(Drug Cartell) ቀጥጥር ስር ያለች አገር ልትሆን በቃች።

ይህ ዓለም አቀፋዊ የብድር መስፋፋትና የሶስተኛው ዓለም አገሮች በካፒታል ገበያ ላይ ጥገኛና ተበዝባዥ መሆን በአፍሪቃ አገሮች ውስጥ ልዩ ቦታ ይኖረዋል። ብዙ የአፍሪቃ አገሮች የተበዳሪነትን ችሎታ(credit worthy) ማሟላት ስለማይችሉ ይበደሩ የነበረው ከኢንዱስትሪ አገሮችና ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በተለይም ከእነ አይ ኤምኤፍ ከመሳሰሉት ነው። ይኸኛው ከዚያኛው የሚለየው እንደነ አይ ኤምኤፍ  የመሳሰሉት የበለጠ በየአገሮች ገብቶ ለመፈትፈትና በቀጥታ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ለማጠናቀር ያመቻቸዋል። ከጋና እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ተግባራዊ የሆኑትን የኒዎ ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለተመለከተ ዛሬ እንደምናየው ውጤቱ አደገኛ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ልንወጣ የማንችለው ሁኔታ ውስጥ ከትቶናል። ያም ሆነ ይህ አንድ አገር በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የግዴታ የመሳተፏን ያህል የግዴታ የተወሰነ ብድር ያስፈልጋታል። ዕዳው ግን የአገሩን የኢኮኖሚ ዕድገት የማያቃውስና ሀብትን የማያባክን እንዲሁም ደግሞ ህብረተሰቡን የማያዘበራርቅና ፍጥጫን የማያስከትል መሆን አለበት። በአንድ አገር ውስጥ ጤናማ ዕድገት ሊመጣና ብድርም አጋዥ ሊሆን የሚችለው በተለይም ከ1973 ዓ.ም ወዲህ በተፈጠረው የፊናንስ ገበያ መሰረት አይደለም። የሁሉንም አገሮች ጥቅም እንደ የሁኔታው ሊያስተናግድ የሚችል አዲስ የፊናንስ ገበያ(financial architecture) ሲዋቀርና እንደነ አይ ኤምኤፍና የዓለም ባንክ የመሳሰሉት አፍራሽ ድርጅቶች በየአገሮች እየገቡ እንደፈለጉት የመፈትፈት ዕደል እንዳያገኙ ሲደረግ ብቻ ነው።

ከብድር ፖሊሲ ወደ ካፒታሊዝም!!

አዲሱን የቁማር ጨዋታ(speculation) ለመረዳት በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከ1945 ዓ.ም ወዲህ የተፈጠረውን አዲስ የኃይል አሰላለፍና የስራ ክፍፍል እንዲሁም ደግሞ የፊናንስ አወቃቀር በመጠኑም ቢሆን መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።  ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ በአሸናፊነት ስትወጣ ራሷ በምትፈልገው መልክ የዓለምን ገበያ ለማዋቀር አመቺ ሁኔታ ነበራት። 70%  የሚሆነው የዓለም ወርቅ ክምችት የአሜሪካን ሴንትራል ባንክ ውስጥ ይገኝ ነበር። ሁለተኛ፣ አሜሪካ በቀጥታ በጦርነት ውስጥ ስላልተካፈለች ኢኮኖሚዋ አልወደመም ነበር። ከሌሎቹ አገሮች ጋር ስትወዳደር የውስጥ ገበያዋም ሆነ የቴክኖሎጂ ዕድገቷ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር። በዚህ ላይ ደግሞ በፖለቲካውም ሆነ በሚሊታሪ መስኩ አይላ የምትገኝ አገር ነበረች። በዚህ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ፣ በተለይም ደግሞ የንግድ ልውውጥና የዶላር ሚና በሷ ፍላጎት የሚደነገግና ፍላጎቷን የሚያንፀባርቅ እንደሆን ሆኖ ሊዘጋጅ ችሏል። የዶላር ሚና ዐይነተኛን ቦታ መያዝ በተለይም ሌሎች የኢንዱስትሪ አገሮች ገንዘባቸውን ከዶላር ጋር በማያያዝ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ዶላር ከወርቅ ጋር በመያያዝ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ዋናው የንግድ መገበያያ ገንዘብ ሊሆን በቅቷል። ዶላርም ሆነ ሌሎች የኢንዱስትሪ አገር የውጭ ከረንሲዎች ተለዋዋጭ መሆናቸው ቀርቶ በተወሰነ ክልል ውስጥ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ (managed fixed exchange rate system) ለዓለም ንግድ ማበብና መስፋፋት አመቺ ሁኔታ እንደፈጠሩ የማይታበል ሀቅ ነው። አሜሪካንም ባላት ሚና መሰረትና ኮሙኒዝምን ለመዋጋት ባላት የጠበቀ ፍላጎት የምዕራቡ ኢኮኖሚ አይሎ እንዳይወጣ ከነበራት አፍራሽ ተግባሯ በመቆጠብ- የመጀመሪያው ዕቅዷ የቀረውን የጀርመንን ኢንዱስትሪ ድምጥማጡን ማጥፋትና የእርሻ አገር ብቻ ማድረግ ነበር- ብዙ ሀብት ወደ አውሮፓ በማፍሰስ በጦርነቱ የፈራረሰው ኢንዱስትሪና ኢኮኖሚ መልሶ እንዲገነባ ያልተቆጠበ ሚና ተጫውታልች። እንደነ ጀርመን የመሳሰሉት አገሮች አሰራአምስት ዐመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውንና የፈራረሱትን ከተማዎች መልሶ በመገንባት በአንድ በኩል የውስጥ ገበያው ሲዳብር በሌላ ወገን ደግሞ ዕቃዎችን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግና ብዙ ዶላር ለማከማችት ቸለዋል። በተለይም ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ጀርመንና ጃፓን በውጭ ንግዳቸው አሜሪካንን እየቀደሙ በመምጣት የዓለምን ገበያ መሻማት ይጀምራሉ። አብዛኛዋን ሀብቷን በሜሊታሪና በኤንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ እያፈሰሰች የመጣችው አሜሪካ በጃፓንና በጀርመን ትቀደማለች ። በዚህም ምክንያት የዶላር ክምችት በአውሮፓ ውስጥ እያደገና ከአሜሪካን ቁጥጥር ውጭ እየሆነ ይመጣል። በተጨማሪም በቬትናም ጦርነት በመወጠሯ ዶላርን በብዛት በማተም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሽከረከረው ገንዘብ አሜሪካ ልትለውጠው ከምትችለው ወርቅ በላይ እየሆነ ይመጣል። በብሬተንስ ወድስ ስምምነት መሰረት ከአሜሪካ ውጭ የሚገኘውን ዶላር አሜረካ በወርቅ የመለወጥ ግዴታ ነበረባት። ከ1960 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ግን አሜሪካ ግዳጇን ልታሟላ አልቻለችም። ሁኔታውን ረገብ ለማድረግ የተወሰዱት ስብሰባዎችና ስምምነቶች በሙሉ የአሜሪካንን የውጭ ንግድ መዛባት ረገብ ሊያደርጉት አልቻሉም። ስለሆነም የፕሬዚደንት ኒክሰን አስተዳደር በ1971 ዓ.ም ወርቅን በዶላር ለመለወጥ እንዳማይችል ያስታውቃል። በ1973 ዓ.ም ዶላር ከሌሎች ጠንካራ ገንዘቦች ጋር ሲወዳደር ዋጋው ዝቅ እያለ ይመጣል። የዶላር ዋጋ ዝቅ ማለት ከውጭ ንግድ አንፃር ለአሜረካን የሚያመች ቢሆንም እየተቦረቦረ የመጣው የአሜሪካ ኢኮኖሚ የበላይነት ሊገታ አልቻለም። አሜሪካን ከአንድ ኢኮኖሚ ቀውስ ወደ ሌላ በመግባት ቢያንስ የኢኮኖሚ የበላይነቷን እያጣች መጣች።

አዲስ የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ የኃይል አሰላለፍና የከረንሲዎች ልውውጥ ቋሚ መሆኑ ቀርቶ ዋጋው በገበያ ላይ በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል መደንገጉ ብዙ ከረንሲ በየሰዓቱና በየቀኑ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የሚሽከረከር ሊሆን ቻለ። በየጊዜው በከረንሲዎች መሀከል የሚታየውን የዋጋ ዝቅና ከፍ ማለት ለመጠቀም(arbitrage)የገንዘብ ከበርቴዎች ገንዘባቸውን በተጨባጩ ኢኮኖሚ ላይ ኢንቬስት ከማድረግ ይልቅ ወደ ቁማር ጨዋታ ገቡ። በዚህም ምክንያትና በየጊዜው በወለድ ከፍና ዝቅ ማለት የተነሳ የዓለም የፊናንስ ገበያ ከምን ጊዜውም የበለጠ ተጎጂ በመሆን በተጨባጩ ኢኮኖሚና በጠቅላላው ከፊናንስ ጋር የተያያዘው የቁማር ጨዋታ መሀከል የሰማይና የምድርን ያህል ርቀት እየታየ መጣ። ይህንን ሁኔታን ለመቆጣጠር አዳዲስ መሳሪያዎች ቢዳብሩም የፊናንስ ገበያውን ከጠቅላላው የምርት ክንውን ጋር ሚዛናዊ ሆኖ እንዲጓዝ ዕድል አልሰጠውም።

በ1980 ዓ.ም ቦታውን የወሰደው የፕሬዚደንት ሬገን መንግስት አዲስ የውስጥና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ፖሊሲ መከተል በማመን የኒዎ ሊበራሊዝምን (The Washington Consensus) ርዕዮተ ዓለም አርማ በማንሳት ሁሉም አገሮች እንዲከተሉት ያደርጋል። በዚህ በአዲሱ የነፃ ገበያ ፍልስፍና ፖሊሲ መሰረት የዓለም ንግድ ብቻ ሳይሆን የካፒታል ገበያ ልቅ እንዲሆን ይደረጋል። በፕሬዚደንት ሩዝቬልት በ1933 ዓ.ም በንግድ ባንክና በኢንቬስትሜንት ባንኮች መሀከል የነበረው የስራ ክፍፍል ግልጽ ሆኖ ያስቀመጠውና የንግድ ባንኮችም በስፔኩሌሽን ውስጥ እንዳይገቡ ያገደው ግላስ-ስቴጋል(Glass-Steagal Act) በሁለት የሴናት ተወካይች ተዘጋጅቶና ተግባራዊ እንዲሆን ሁኖ የወጣው ህግ እንዲፈርስ በማድረግ የንግድ ባንኮችም በተዘዋዋሪ የቁማር ተጫዋች ተካፋይ እንዲሆኑ መንገድ ይከፈትላቸዋል። ይህ ልቅ አዲስ የካፒታል ገበያ(capitalmarket) ለኒዎ ሌበራል ኢኮኖሚስቶች ሁኔታውን በማመቻቸት አዳዲስ የፊናንስ ዘዴዎችን(financial instruments)በመፍጠር የገንዘብ ካፒታል ከተጨባጩ ኢኮኖሚ(real economy)ተላቆ ብቻውን እንዲሽከረከር መንገዱን ያዘጋጃሉ። በዚህም ምክንያት የኢንዱስትሪን ዕድገት ለማስፋፋትና ምርትን ለማምረት መጠቀሚያ የነበረው የካፒታል ገበያ ሚና(primary market) ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር የካፒታል ገበያው ለሁለተኛው ገበያ(secondary market)መድረኩን በመልቀቅ የኢንድስትሪ ድርሻ ማረጋገጫ(stock market paper)ይህ ዋናው መገበያያ መድረክ በመሆን ወረቀቱ ከአንድ እጅ ወደ ሌላ በመሸጋገር ከተጨባጩ ኢኮኖሚ እየተነጠለ በመምጣት በተለይም ለደራሽ ኢኮኖሚስቶች ከሰፊውና ከየዋሁ ህዝብ ገንዘብ መምጠጫ መንገድ ሊሆን በቅቷል። እነዚህም በቀላሉ ሀብታም ሲሆኑ ቁማር እጫወታለሁ ብሎ በመጓጓት ገንዘቡን እየከሰከሰ የኢንድስትሪ ድርሻ ወረቀት የገዛ የመሰለው ራቁቱን እንዲሄድ ተገዷል። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ እየሰፋ የመጣው የካፒታል ገበያ እጅግ የተወሳሰቡ የፊናንስ መሳሪያዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ የገንዘብ ሚናና ሀብት ማካበት እንዲሁም ደግሞ ገንዘብን በገንዘብ ኃይል ማከማችትና መበልጸግ የሚለው እያየለ በመምጣቱ የካፒታል ገበያ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት ብዙ አገሮችን እያሳተፈና ኢኮኖሚያቸውንም እየተቆጣጠረ መጣ። በተለይም በ1997 ዓ.ም የብዙ ኤሺያ አገሮችን ሀብት የጠራረገውና በአንድ ወቅት ሀብታም የነበሩ ወደ ሱቅ ባልደረቤነት በመለወጥ ተራ ነጋዴ የሆኑት በዚህ የቁማር ጨወታ ውስጥ በመግባታቸው ነው። ይህ ሳይንስ የሚመስለው የተወሳሰበ የማቲማቲካል ሞዲል በመሰረቱ በምንም ዐይነት ከሳይንስ ጋር የማይገናኝና ህብረተሰብአዊ ችግርን የማይፈታ እንደ አሜሪካ የመሳሰሉትን አገሮች ሳይቀር ከኢንዱስትሪ ካፒታሊዝም ወደ ካሲኖ ካፒታሊዝም እንዲለወጡ በማድረግ አዳዲስ የስራ መስክ ለመክፈት ያለው ኃይልና ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት ለመፍጠር ያለው ችሎታ እዚህ ግባ የማይባል ሆነ። እነዚህ አዳዲስ የፊናንስ መሳሪያዎች ከነበሩት የፊናንስ መሳሪያዎች ጋር በመጣመርና „እየተሻሻሉ“ በመምጣት ለካፒታል ገበያው ልዩ እምርታ በመስጠት ሁኔታውን ውስብስብ በማድረግ ከቁጥጥር ውጭ መጡ። ለምሳሌ ካሉት የፊናንስ ገበያ መሳሪያዎች የፈለቀው ወይም የዳበረው(derivatives) ንጹህ የቁማር ጨዋታ በመሆን በሁለት የቁማር ተጫዋቾች መሀከል እንደሚካሄድ ዐይነት የሀብት መሸጋሸጊያ መንገድ በመሆን አንደኛውን በአንድ ጊዜ ሀብታም ሲያደርገው ሌላውን ደግሞ ሀበቱ እንዲሟጠጥ ያደርጋል።ለምሳሌ የዶላር ዋጋ ወይም የዘይት ዋጋ በበርሜል ወይም ደግሞ አንድ ላይ ተጣምሮ የሚሰላ የፊናንስ ገበያ(indicies) ዋጋው ከተወሰነ ቀናት ወይም ወራት በኋላ ሊያድግ ይችላል በሚል ወይም የዶላር ወጋ ወይም ሌላ ካረንሲ በዚህ መጠን ዝቅ ሊል ይችላል በሚል ብዙ ቢሊዮን ዶላር በማፍሰስ ይወራረዳሉ። በዚህ ዐይነት ጨዋታ ውስጥ የሚሳተፉ ኢንቤስትሜንት ባንኮች ኢንስቲቱሽናል ኢንቬስተርስ ከሚሏቸውም እንደ ንግድ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተጨማሪ ብድር በመውሰድ ለጨዋታው ልዩ ዕምርታ በማከል የኪሳራውም ሆነ የዕድሉ ተካፋይ ብዙ ኃይሎች እንዲሆኑ ይገደዳሉ ማለት ነው። በዚህ ምክንያት የንግድ ባንኮችና የኢንሽራንስ ኩባንያዎች ሚናቸውን በመርሳትና በመንግስታት የተከፈተላቸውን ሀብትን የማሸጋሸግ ቀዳዳ እየተጠቀሙ የብዙ ሚሊዮን ህዝብ ሀብት እንዲባክን ያደርጋሉ። በአንፃሩ ደግሞ በዚህ ዘዴ የተጠቀሙት አዲስ ኢኮኖሚስቶች የራሳቸውን ምሽግ በመመሸግ የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ሌላ ሀብት ማምጫ ዘዴ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ማረጋገጫ(Hedge Fund) ሌላው ማጭበርበሪያ ዘዴ በጥንታዊ መልኩ ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን እንደ ዘይት የመሳሰሉት ስትራተሬጂክ ጥሬ ሀብቶች የሚገዛበትና ጠቅላላው የዓለም ጥሬ-ሀብት በጥቂት ከበርቴዎችና በኢንዱስትሪ አገሮች ቁጥጥር ስር እንዲውል የሚደረግበት  የረቀቀ ልዩ የቁማር ጨዋታ ዘዴ ነው። በጥንታዊ መልኩ ሄጅ ፈንድ ማለት በከረንሲ ልውውጥና ዕድገት ምክንያት በሺያጭና በገዢ መሀከል የሚደረግ ልዩ ስምምነት ሲሆን፣ በተስማሙበት የከረንሲ ዋጋ ሻጪው ለገዢው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዕቃውን ወይም እህልን እንዲልክለት ስምምነት ይገባሉ። ስምምነቱን ከተዋዋሉ በኋላ የሚፈጠር የከረንሲ ልዩነት እንደ ዋጋ መተመኛ አይሆንም ማለት ነው። ይህ ጥንታዊ ጤናማ የገበያ መነገጂያ ዘዴ አሁን ወደ ንጹህ ቁማር ጨዋታ በመለወጥ በተለይም እንደዘይት የመሳሰሉት አስፈላጊ ጥሬ ሀብቶች ከስድስት ወር በፊት ቀደም ብሎ በመግዛት በዓለም ገበያ ላይ የዘይት ዕጥረት ያለ በማስመሰል የነዳጅ ዋጋ ከሚገባው በላይ ከፍ እንዲል በማድረግ በተለይም መጠነኛ ገቢ ያለው ህዝብ እንዲሰቃይ ያደርጋሉ። ይህ ቀደም ብሎ የሚደረግ የገበያ ስምምነት(future market deals) ለስንዴና ለዘይት እንዲሁም ደግሞ ለሌች ስትራቴጂክ ጥሬ ሀብቶች መወደድ ምክንያት ሊሆን በቅቷል ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት በዓለም ላይ ተሰራጭተው የሚገኙ ብዙ ስትራቴጅክ ጥሬ ሀብቶች በነዚህ ኢንቬስትሜንት ባንኮች ቁጥጥር ስር እየዋሉ በመምጣት አሁን ደግሞ እንደ ቻይናና ሌሎች የአረብ አገሮች ተካፋይ በመሆን ባላቸው ሀብት (state funds) እየተመኩና ቁማር እየተጫወቱ የዓለምን ህዝብ ኑሮና የገንዘብ ገበያ እያናጉ ነው።

እነዚህ አዲስ ኤንቬስትሜንት ባንኮች በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ የትላልቅ ኢንዱስትሪዎችንና የመገናኛ መስመሮችን ድርሻ(shares) በመግዛትና ወሳኝ ሚናን በመጫወት ለስራ መስክ መፈናቀልና ኢንዱስትሪዎች ከአንድ ቦታ ተነቅለው ወደ ሌላ ቦታ እየወሰዱ በመትከል ህብረተሰብአዊ ሚዛንን በማዛባት የትርፍ ትርፍን እያካበቱ ነው። በዚህም ሳይወሰኑ ህንፃዎችንና ቤቶችን በመግዛት ካደሱ በኋላ የቤት ኪራይ እንዲጨምር በማድረግ ለብዙ ዐመታት ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ ተከራዮች እንዲፈናቀሉና ባልባሌ ቦታ እንዲኖሩ እየተገደዱ ነው። በዚህም ምክንያት እንደ ለንደንና ፓሪስ እንዲሁም ሞስኮውና ኒዎርክ ለመኖር የማይቻለበት ቦታ ሲደረስ፣ የከተማ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ በእነዚህ እንደ አንበጣ ቀንጥሰውና ድምጣመጡን አጥፍተው የሚጠፉ የዘመኑ ደራሽና ምንም ዐይነት ስነ-ምግባር የሌላቸው እዚህና እዚያ እንደ ዘላን የሚሽከረከሩ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እየዋለ መጥቷል። ዓለም ዛሬ ኢንቬስትሜንት ባንኮች ተብለው በሚጠሩ በተለይም ቋሚነታቸው አሜሪካ የሆኑ ቁጥጥር ስር ወድቃለች። የዓለም ስትራቴጂክ ጥሬ-ሀብቶች በነዚህ ባንኮች ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። የእነዚህ ከኢንዱስትሪ ካፒታሊዝም ጋር መገናኘትና መንግስታትን መቆጣጠር ዛሬ ለምናየው የእርስ በርስ ጦርነት ለሚመስለው የወንድማማቾች ጦርነት ዋና መነሻ ሆኗል። አገራችንም የዚህ ሰለባ በመሆን እነዚህ ኢንቬስተሮች መጥተው ኢንቬስት እንዲያደርጉ የኢህአዴግ መንግስት መንገዱን አመቻችቶላቸዋል።

ከ1980ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ልቅ እየሆነ የመጣው አዲሱ የካፒታል ገበያ ይህንን ሲመስል ፖሊሲውን የሚያራምዱት አገሮችና መንግስቶቻቸውም የዚህ ሰለባ በመሆን ለስራ መስክ መፈራረስ፣ ለዓለም ንግድና ምርት መቀዝቀዝ እንዲሁም ደግሞ ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ በእኩልነት እንዳይስፋፋና የዓለም ህዝቦች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አግዷል። በዚህ አዲስ የፊንስ መሳሪያና ገበያ እንዲሁም የቁማር መጫወቻ ዘዴ ከንግድና ከምርት ጋር ያልተያያዘ በየዕለቱ ከ1.5 ትሬሌየን እስከ 3 ትሬሊየን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሽከረከር፣ ዕቃንና አገልግሎትን በዓለም ገበያ ለይ ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት 600 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ይወጣል ወይም በዚህ የሚገመት ዕቃና አገልግሎት ይሸጣል። በዚህም ምክንያት በገንዘብ ገበያ ዕድገትና በቁማር ጨዋታ መሀከል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በፊዚካል ኢንቬስትሜንት መሀከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችና ድልድዮችን ማደሻ እንዲሁም ደግሞ ለሰው ልጅ መኖሪያ የሚያገለግሎ መኖሪያ ቤቶችን መስሪያ ገንዘብ ሲጠፋ በአንፃሩ ግን ገንዘብ የቁማር መጫወቻ በመሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ይሰቃያል። በፊዚካል ኢንቬስትሜንትም ዝቅ እያለ መምጣት በብዙ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለአደጋ መጋለጥ ብቻ ሳይሆን የየአገሩ መንግስታት ከቀረጥ የሚገኝ በቂ ገቢ ማግኘት ስለማይችሉ አስፈላጊውን ለህዝቦቻቸው ማድረግ የሚገባቸውን እንደ ጤና መስክ መስፋፋትና ድልድዮችን መጠገን ወይም ደግሞ ለወጣቱ የስራ መስክና የባህል ማዕከል ለመክፈት የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ይህ ሁኔታ በተለይ በአሜሪካ በመስፋፋቱና ድልድዮችም በየጊዜው ስለማይጠገኑ ትላልቅና ከባድ መኪናዎች በሚያልፉበት ጊዜ ስለሚገረመሱ ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ መጥቷል። ስለሆነም ከ1980ዎቹ ጀምሮ እያደገና እየተስፋፋ የመጣው የቁማር ጨዋታ በጥቂት አገሮች ላይ ብቻ ሳይወሰን ብዙ አገሮችን በማቀፍ በቢሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ ዕድል እየወሰነና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልን እያመጣ ነው። ይህንን የፊናንስ ገበያ ውስብስበነትና የሚያመጣውን አደጋ የተገነዘቡና ብዙ ምርምር ያደረጉ ኢኮኖሚስቶችና ፈላስፎች ኢንዲሁም ሳይንቲስቶች የግዴታ የዓለም የፊናንስ ገበያ በዚህ መልክ መቀጠል እንደሌለበትና ከዶላር ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሌሎች ጠንካራ ካረንሴዎችን ያቀፈ የመገበያያ ከረንሲ በመፍጠር የዓለም ንግድና ምርት እንዲሁም ገንዘብ ለቁማር ጨዋታ መሆኑ ቀርቶ ለተጨባጭ ኢንቬስትሜንት በመዋል የብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ኑሮ እንዲሻሻል ጉትጎታ ያደርጋሉ። በሌላ ወገን ግን የኢንዱስትሪ አገሮች በተለይም ደግሞ አሜሪካ የቀረውን የበላይነትዋን ላለማጣት ስትል ነገሩን ተግባራዊና ተደማጭነት እንዳይኖረው የማይሸርቡት ተንኮል ይህ ነው አይባልም። በፊናንስ ኦሊጋርኪዎችና በመንግስታት መሀከል የተመሰረተው ያልተቀደሰ ጋብቻ በፊናንስ ገበያ ላይ ዐይነተኛ ለውጥ እንዳይመጣ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሯል።

የኢንዱስትሪ አገሮች መንግስታት በህገ-መንግስት ውስጥ የሰፈረውንና የሰፊውን ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቀውን አንቀፅ በመርገጥና ለኢንዱስትሪና ለፊናንስ ከበርቴዎች በመንበርከክ በሚያደርጉት የተዛባ ፖሊሲ የብዙ ህዝቦች ዕድል እየጠመመና ሀብቶቻቸውም እንዲሟጠጥ እያደረጉ ነው። ለባንኮችና ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተሰጠው የነሱን የመደራደርና የማጭበርብር ኃይል የሚያጠናክር ሰርዓት(policies) ሰራተኞት ከአርባ ዓመት ስራ በኋላ ጡረታ በመክፈል ያጠራቀሙትን ገንዘብ እንዳያገኙ በዚህም በዚያም በመቆራረጥ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ እየገፈተሯቸው ነው። በተለይም በየጊዜው ኢኮኖሚስት ነን በሚሉ የኒዎ ሊበራል ርዕዮተ ዓለም አራማጆች እየረቀቀ የሚወጣው የማቲማቲክ ሞዴል የሚከፈለው የጡረታ አበል እየቀነሰ የሚሄድ የሚያደርግ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ ተጨማሪ በካፒታል ገበያ ላይ የሚደገፍ የጡረታ አበል መክፈል አለባችሁ ካለበለዚያ ጡረታ ስትገቡ የምታገኙት ገቢ አይበቃችሁም እያሉ የማያስፈልግ ምክር በመምከር ሰዎችን ያስፈራራሉ። እንደሚታወቀው በካፒታል ገበያ ለይ የሚቀመጥ ገንዘብ አስተማማኝ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ባንኮች ራሳቸው ኢንሹራንስ እስካልገቡ ድረስ ገንዘቡ ተሟጦ ሊጠፋ እንደሚችል በተለይም የአሜሪካን ልምድ ያስተምረናል። የሚገርመው ነገር ደግሞ እራሳቸው ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም የከሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

አሜሪካን በዕዳ የተሰሩ ቤቶች ቀውስና መዘዙ

በብዙ ትሬሌዮን ዶላር የሚቆጠር በዕዳ የተሰሩ ቤቶች ላይ የደረሰው ቀውስ ካላፈው ሰኔ 2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተከሰተ የመጣ ሲሆን በዓለም ላይ አሉ የሚባሉትንና ትላልቅ የአሜሪካንን ኢንቬስትሜንት ባንኮችን እንደ ቤር ስቲርስንና(Bear Stears) ሲቲ ግሩፕስ የመሳሰሉትን አልፎ ወደ ጀርመንና ወደ ስዊዘርላንድ በመዝለቅ የመንግስትንም ሆነ የንግድ ባንኮችን እስከማናጋት ደርሷል። እንደቤር ስቲርስ የመሳሰሉት ኤንቤስትሜንት ባንኮች በተለይም ከንግድ ባንኮች በቅናሸ ዋጋ የገዟቸውን ቤቶች በተጨማሪ ከኢንቲቱሽናል ኢንቬስተርስ-የንግድ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲሁም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ- የሰበሰቡትን ገንዘብ በዚህ አስተማማኝ ባልሆነ በብድር የተሰራ ቤት ላይ ኢንቬስት ያደርጋሉ። ይህ ከባንክ ህግ ውጭ የሆነ የብድር አሰጣጥ ዘዴ፣ ተበዳሪዎቹ ቢያንስ 25%  የሚያህል ካፒታል ሳይኖራቸው የተሰጣቸው ብድር የኋላ ኋላ ኢንቬስትማንት ባንኮች ሊወጡ የማይችሉበት ማጥ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በተጨማሪ የአብዛኛው የአሜሪካ ህዝብ የመቆጠብ ኃይሉ (saving rate) ካለፉት ስላሳ ዐመታት ጀምሮ እየተናጋ በመምጣቱና አብዛኛውም ህዝብ በክሬዲት ካርድ ስለሚከፍል ተበድሮ የሰራውን ሆነ የገዛውን ቤት ዕዳ መልሶ ሊከፍል የማይችለበት ሁኔታ ተከስቷል። በመሀከሉ የብድሩ ወለድ እየጨመረ በመምጣቱ ቀውሱን ሊያባብሰው ችሏል።  በመሆኑም እንደ ደም ዝውውር መሽከርከር የሚገባው በባንኮችና በተበዳሪዎች መሀከል ያለው በየጊዜው ወለዱንና የዋናውን ካፒታል አካል መክፈል መቋረጥ ሲጀምር፣ ኢንቬስትሜንት ባንኮችም ሆነ የንግድም ሆነ የመንግስት ባንኮች የልቡ ትርታ መምታት ወደ ማቆም እንደደረሰ ሰው ይሆናሉ። በየጊዜው መከፈል ያለበት የጠቅላላው ዕዳ ክፍል በመቋረጡ ትልልቅ የአሜሪካንን ኤንቬስትሜንት ባንኮችን ሲያናጋ ማገገም የቻሉት በአሜሪካን የፌዴራል ሪዘርብ ገንዘብ ፍሳሽ ብቻ ነው። ይህ ራሱ ከህግ ውጭ የሆነ አሰራር – የሴንትራል ባንክ የንግድ ባንኮችን ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮችን ብቻ እንጂ ማዳን ያለበት ቁማር የሚጫወቱትን ገንዝብ በማፍሰስ ነፍስ እንዲዘሩ ማድረግ አይገባውም-ለጊዜው የኢንቬስትሜንት ባንኮችን ይወት እንዲያንሰራሩ ቢያደርግም ዐይነተኛ ቀውሱን ግን ሊፈውሰው አልቻለም። በተጨማሪም ከንግድ ባንኮች በርካሽ የተገዙ የቤት ዕዳዎች(securitization)- ለምሳሌ ተበዳሪዎች ከንግድ ባንኮች ተበድረው ቤት ይገዛሉ ወይም ይሰራሉ፤ የንግድ ባንኮች ተበዳሪው ገንዘቡን በጊዜው መክፈል የማይችል መስሎ ከታያቸው ዕዳውን ረከስ አድርገው ለኢንቬስትሜንት ባንኮች ይሸጡላቸዋል። አሁን ግኑኝነቱ በንግድ ባንክና በተበዳሪዎች መሀከል መሆኑ ቀርቶ በተበዳሪዎችና በኢንቬስትሜንት ባንኮች መሀከል ይሆናል። በዚህ መልክ እየተወሳሰበ የመጣው በተበዳሪዎችና በባንኮች መሀከል ያለው ግኑኝነትና የኢንቬስትሜንት ባንኮች ከፍተኛ ትርፍ እናጋኛለን በማለት ያወጡትና ከተጨባቹ ሁኔታ የራቀ ሞዲል ነገሩን የባሰ ውስብስብና ዕዳው ሊከፈል ያልቻለበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሁኔታው ግን ይህ ሳይሆን ከላይ የተገለጸው ጠቅላላው የኢኮኖሚ ዘርፍ መናጋት ሲሆን፣ በተለይም የፊናንስ ገበያ እያበጠ መምጣትና ከተጫበጩ የኢኮኖሚ ዘርፍ በመለየቱ የጠቅላላውን ህብረተሰብ የመግዛትና ከንጹህ ገቢ የመቆጠብ ኃይሉን ከስሌት ውስጥ ያላካተተ በመሆኑ ነው። በብዙ ምርምሮች እንደቀረበው የነዚህ የመጤ ኢኮኖሚስቶች የቁማር ጨዋታ ስሌትና መንግስታዊ ቁጥጥር አለመኖር ለቀውሱ ዐይነተኛ ምክንያት ሆነዋል።  ይህ ሁኔታ ውስጣዊ ቀውስ(sytemic crisis) በመፍጠር በሌላ ወገን ደግሞ የፊናንስ አሊጋርኪ የዓለምን ህዝብ ዕድልና ዕድገት እንዲውስን መንገዱ ሁሉ ተመቻችቶለታል።

በሌላ ወገን በተለይም ክፉኛ የተመቱት በከፊልና ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉት የጀርመን ባንኮች በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ኦይሮ በመክሰር በመንግስት ርዳታና በአውሮፓ አንድነት የሴንትራል ባንክ የማገገሚያ ድጎማ ነፍስ ሊዘሩ ችለዋል። እነዚህ የከሰሩት በተለይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የፌዴራል ባንኮች ተግባር ቁማር መጫወት አይደለም። ዋናው ዐላማቸው በተለይም ለትናንሽና ለማዕከለኛ የኢንዱስትሪ ከበርቴዎችም ሆነ በሌላ አትራፊ የንግድ መስክ ለተሰማሩ ብድር በርካሽ ወለድ ማበደርና በየአካባቢዎቻቸው ህብረተሰብአዊ ሚዛን እንዳይዛበ ታሪካዊ ተልዕኮአቸውን መወጣት ነበር። ይህንን ለማድረግ ያልፈለጉትና በአለቆቻቸው እየተገደዱ ለትናንሽ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ማቅረብ የነበረባቸውን ተመጣጣኝ ብድር አስተማማኝ አይደላችሁም በማለት በካፒታል ገበያ ላይ ቁማር መጫወታቸው መጨረሻ ላይ በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉት ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል። በዚህም ምክንያትና በጊዜው የባንኩን ተግባር መቆጣጠር ያልቻሉት የጀርመን የመንግስት ብድር ሰጪ ባንኮች ኃላፊ ከስራቸው እንደሚለቁ አስታውቀዋል። ሰሞኑን ደግሞ እንደዚሁ በዚህ ቁማር ጨዋታ የተሰማሩት የአንድ ፌዴራል መንግስት ዋና አስተዳዳሪ በደረሰባቸው ግፊትና ባደረሱት ኪሳራ ስራቸውን እንዲለቁ ተገደዋል።

በአይ ኤምኤፍ ጥናት መሰረት አሜሪካን አገር በተከሰተው የፊናንስ ቀውስ ምክንያት የተነሳ እስካሁን ድረስ ወደ 945 ቢሊዮን ዶላር ወይም 603 ቢሊዮን ኦይሮ የሚጠጋ በጠቅላላው ኢኮኖሚ ላይ ኪሳራ ደርሷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአሁኑ ወቅት በብዙ ኢኮኖሚስቶች የተደረሰበት ውጤት አሜሪካን በኢኮኖሚ ቀውስ(economic recession)  ውስጥ ስትገኝ አብዛኛውን የአሜሪካንን ህዝብ የኢኮኖሚው ሁኔታ በጣም እንዳሳሰበው ይነገራል። ይህ የፊናንስ ቀውስ መዘዝ ወደ አውሮፓ በመዝለቅ አሁን በተሻለ የኢኮኖሚ ዕደገት ላይ የሚገኘውን የአውሮፓ አንድነትን ኢኮኖሚ እንደሚያዳክመውና ዕደገቱም አሁን ካለበት ወደ 1.4ና ወደ 1.2 በመቶ ዝቅ እንደሚል የአይ ኤምኤፍ ጥናት ያመለክታል።ይህ የሚያሳየን የቱን ያህል በፊናንስ ገበያው ቀውስ የተነሳ የተጨባጭ ኢኮኖሚው ሁኔታም እየተዳከመ እንደመጣና ወደፊትም እንደሚመጣ  ነው።

ይህ ዐይነቱ የተወሳሰበና ልቅ የፊናንስ ገበያ አሰራር አሜሪካን እንደታየው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተበዳሪዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ሲገደዱ ውሾቻቸውም ጌታ በማጣት የየክልል አስተዳዳሪዎች እስኪሰበስቧቸው ድረስ በየሜዳው እንዲቀዋለሉ ተገደዋል። ቤቶችም ገዢ በማጣትና ወደ መፈራረስ በማምራት በአካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ግራ እንደተጋቡ ይታወቃል። ይህ በአሜሪካ የፈለቀው ውስብስብ የፊናንስ ገበያ አሰራርና የብድር አሰጣጥ ዘዴ ከሌሌች ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ጋር በመጣመር የአሜሪካንን ህብረተሰብ እያናጋው በመምጣት ላይ ነው።

በተለይም አሜሪካ ሌሎች አገሮችን እያስገደደ የነፃ ንግድ አባል ሁኑ፤ የነፃ ንግድ መገበያያ ክልል አስፈላጊ ነው እያለ ድርድር ውስጥ የሚገባውና የሚስማማው ራሱንም እየመታው ነው። ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከሆነች ወዲህ የአሜሪካ ገበያ ላይ ርካሽ ምርቷን በማራገፏ የንግድ ሚዛኗ በከፍተኛ ደረጃ እየተናጋ ነው። በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን የንግድ ሚዛን ወደ 900 በሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሚጠጋ ተናግቷል። እንደዚሁም ከካናዳና ከሜክሲኮ ጋር የተመሰረተው የነፃ ንግድ ክልል ስምምነት እንደ ኦሀዮና ፔንስልቬኒያ የመሳሰሉትን የሰራተኞት ከተማዎች እየመታ ነው። የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ርካሽ የስራ ጉልበት ለማግኘት ሲሉ ኢንዱስትሪዎችን እየነቀሉ በመውሰዳቸውና እዚያ በመትከላቸው ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትና የንግድ ልውውጥ እየፈራረሰ ነው። አሜሪካ በዚህ እጅግ ርስ በርሱ የሚቃረን ፖለቲካ የምትከተለው የነፃ ንግድ ፍልስፍና የውስጥ ገበያውንና የማምረት ኃይል ማዳከም ብቻ ሳይሆን አማሪካ ለጦርነትም ሆነ የውጭ ንግድ ኪሳራዋን ለመሸፈን በውጭ ካፒታል እንድትመካ ተገዳለች። በዚህም ምክንያት በየቀኑ ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ካፒታል ወደ አሜሪካ መፍሰስ አለበት። በዚህ ዐይነት ከውጭ የሚመጣው ካፒታል ማደግና ዕዳዋ መቆለሉ ብቻ ሳይሆን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠርም ወለድ በየዐመቱ ለሌሎች አገሮች ማስተላለፍ አለባት። በሌላ ወገን ደግሞ አሜሪካን ባንኮች ውስጥ የተወሰነውን ገንዘባቸውን ማስቀመጥ የተገደዱትና የመንግስት ቦንድ የሚገዙት እንደነቻይና ያሉ አገሮች በዶላር ዋጋ ዝቅ ማለት የተነሳ ብዙ ሀብት እያጡ ነው። ይህንንም በመገንዘብ ሀብታቸውን በአውሮፓ አካባቢ በማስቀመጥ ከኪሳራ ለመዳን ሲሯሯጡ ይታያል።

ይህ ሁሉ የሚያሳየን ግሎባላይዜሽንና የነፃ ንግድ መፈክሮች እንደተዘመረላቸው ለዓለም ህዝብ ዕድገትንና ብልጽግናን አላመጡም። የኢንዱስትሪ አገሮች በተለይም የሶስተኛውን ዓለም ገበያ ለመቆጣጠር በሚያደርጉት አጉል ግብ ግብና ግፊት ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ከቁጥጥር ውጭ እየወጡና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል እየደረሰባቸው ነው። ሰሞኑን የምናየው የእህል እጥረትና የዋጋ ግሽበት ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንገስታት የተሳሳተ የእርሻ ፖሊሲ በመከተላቸውና ከአውሮፓና ከአሜሪካ በሚመጣ ስንዴና በቆሎ በመመካታቸውም ብቻ ሳይሆን በየአገሩ በነፃ ገበያ ስም የተስፋፋው ዕውነተኛ ዕድገትን የማያመጣ ፖሊሲ መንግስታትን አንቆ በመያዙ ነው። በተጨማሪም እየጦፈ ያለው ስፔኩሌሽን ለእህል ዋጋ መወደድ ዐይነተኛ ምክንያት ሆኗል። እንዲሁም በአንዳንድ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የእርሻን መሬት ለአግሮ ዲዝል ማምረቻ ለሚያገለግሉ ሰብሎችና አትክልቶች ማዋል እንዲሁም ጭፍን የጫካ ጭፍጨፋ ተፈጥሮን ከማናጋት አልፎ ለእህል እጥረት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።  ስለሆነም ጭፍን ግሎባለይዜሽንና ቀደም ብሎ ክርክር ሳይደረግበት በጥቂት የዓለም አቀፍ የፊናንስ ኦሊጋርኪዎችና አፈቀላጤዎች የሆኑ ኢኮኖሚስቶች ተግባራዊ እንዲሆን የሚደረገው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የነፃ ንግድ ፍልስፍና ወደ ውስጥ የህብረተሰቦችን የማምረትና በራስ የመመካት ኃይል እያናጋው ነው። የስራ ክፍፍል እንዳይዳብርና ህብረተሰብአዊ መተሳሰር እንዳይኖር እንቅፋት ሆኗል። ለባህል ዕድገትና ለብሄራዊ ነፃነት መከላከል እንቅፋት እየሆነ ነው። ሰሞኑን እንደምናየው በተለይም ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ምስቅልቅል ውስጥ እየገቡና ህብረተሰቦቻቸውም ከቁጥጥር ውጭ እየወጡ ነው።

ግሎባላይዜሽንና የእኛ ዕጣ !!

ኢትዮጵያ በግሎባላይዜሽን መዳፍ ስር ይበልጥ እየወደቀች የመጣቸው በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ነው። በተለይም ከ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ በአፄ ኃይለ ስላሴ መንግስትና አገዛዝ ብዙም ሳይታሰብበት የተወሰደ አንድ ወጥና የተኮላሸ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ የገንዘብ ኢኮኖሚ እንዲስፈፋ ከማድረጉ በስተቀር ዕውነተኛ ሀብት እንዲዳብርና አገሪቱም ዕውነተኛ የስራ ክፍፍልና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ቴኮኖሎጂያዊ ምጥቀት እንዲመጣ ሊያግዝ እንዳልቻለ የህብረተሰብ ሳይንስን ላጠናና ሁኔታውን ለተከታተለ ግልጽ ነው። በመሆኑም እየተስፋፋ የመጣው ብዙም ከምርት ጋር ሳይሆን ከንግድና ከአገልግሎት ጋር የተያያዘው የገንዘብ እንቅስቃሴ (monetary economy) የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በማዛነፍ ዕውነተኛና በአስተሳሰቡ እየዳበረ ሊመጣ የሚችል የከበርቴ መደብ ብቅ ብሎ ሁኔታውን እንዲያመቻች ዕድል አልሰጠውም። አገዛዙ ከውጭ ከበርቴዎች ጋር በመቆላለፍ የወሰደው የኢኮኖሚ ግኑኝነት፣ በአንድ በኩል የፊዩዳሉን ስርዓት በልዩ መልክ ሲያጠነክረው፣ በሌላ ወገን ደግሞ የውጭ ከበርቴዎች የአገዛዙን ፖለቲካዊና ህብረተሰብአዊ አስተሳሰብ ድክመት በመገመት የአገሪቱን የዕድገት አቅጣጫ መወሰን ቻሉ። በዚህም የተነሳ በጣምራ ከመንግስት ጋር የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ሄደት በውጭ ከበርቴዎች ፍላጎት የሚካሄድ እንጂ የአገሪቱን ፍላጎት በማካተትና ሀቀኛ ህብረተሰብአዊ የስራ ክፍፍል በማዳበር ህብረተሰብአዊ መተሳሰር እንዲኖር ሊያደርግ የሚችል አልነበረም። የኢንዱስትሪዎችን የአስተዳደር ሁኔታ ስንመለከት በአስተዳደር በኩል የኢትዮጵያ ማኔጀሮች ተሳትፎ ዝቅተኛ ሲሆን፣ እንዴት፣ ለማንና ምን እንደሚመረት ይወሰኑ የነበሩት 49%  ብቻ ድርሻ የነበራቸው የውጭ ከበርቴዎች ነበሩ።

በዚህም ምክንያት ይህ ዐይነቱ የአስተዳደር አወቃቀርና ውስጠ-ኃይል(dynamism) የሌለው የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ህብረተሰብአዊ ዝብርቅርቅነትን በማምጣት ወደ ፊት ሊፈነዳ የሚችልን ሁኔታ አዘጋጅቶ አለፈ። ለምሳሌ በተበላሸ ፖሊሲው ምክንያት የተነሳ ወደ ከተሞች እየተሰደደ የመጣው የተወሰነው የገጠሩ ህዝብ አዲስ የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ባለማግኘቱ ወደ አልባሌ ቦታዎች እንዲሰማራ ተገደደ። የተወሰነው ክፍል በተለያዩ ዝቅተኛና ዕውነተኛ ሀብት ሊፈጥሩና ሊያከማቹ የማይችሉ የኢኮኖሚ አውታሮች (informal sector) ውስጥ ገብቶ ዕድሉን ሊያቃና ሲሯሯጥ፣ ሌላው ደግሞ ወደ ሌብነት፣ ማጅራት መችነትና ሴተኛ አዳሪነት በመሰማራት ተፈጥሮአዊ የማሰብ ኃይሉን እንዳይጠቀም ታገደ። በሌላ ወገን ደግሞ ባለው ህብረተሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ (social and eocnomic status) ተደስቶ የሚኖረው ቢሮክራሲያዊ ኃይል ለዚህ አዲስና አደገኛ ሁኔታ መልስ ሊሰጥ የሚችል ሆኖ እራሱን ሊያዘጋጅ አልቻለም። ባለው የተሻለ ሁኔታ በመደሰትና እራሱን ከህብረተሰቡ እያገለለ በመምጣት የህብረተሰቡ አለኝታ ከመሆን ይልቅ የውጭ ኃይሎች ተላላኪ በመሆን ወደ ወስጥ ዕወነተኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም ዕድገት እንዳይመጣ አገደ። እንደዚህ አይነቱ ሁኔታ በብዙ የላቲን አሜሪካ አገሮችና በአፍሪቃ ምድር የተከሰተ ሲሆን፣ ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለዚህ ተጠያቂው በዓለም ላይ የበላይነቱን የተቀዳጀው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደሆነ ይታወቃል።

የተማሪው እንቅስቃሴ ሲጀምርና እያየለ ሲመጣ በመሰረቱ ይህንን የተኮላሸ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ለማሰተካከል ነበር። የተነሱትም ጥያቄዎች በዛሬው ዐይን ስር-ነቀል(radical) ናቸው ተብለው ቢገመቱም፣ በጊዜው በነበረው ዓለም አቀፋዊ የአስተሳሰብ ሁኔታና ከአገራችንም ዕውቀት አንፃር ሁኔታ ስንነሳ ከዚህ አልፎ ሊሄድ የሚችል አልነበረም። የተማሪው እንቅስቃሴ ያነሳቸው ጥያቄዎችና በከፊል ተግባራዊ እየሆኑ የመጡት አስፈላጊውን ውጤት ሊያመጡ ያልቻሉት፣ በአንድ ኃይል ጥፋት ሳይሆን፣ በተለይም ለውጥ እንዳይመጣ ከአሜሪካን ጋር ያበረው የቀኝ ኃይልና ነፃ እንወጣለን ብለው እዚህና እዚያ የሚራወጡት፣ በመሰረቱ ታሪክን ያልተገነዘቡ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያ ሊሆኑ የበቁ የብሄረ-ሰብ እንቅስቃሴዎች በከፈቱት ጦርነት ምክንያት የተነሳ ነው። ብዙም ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና የሌለውና የታሪክን አረማመድ በቅጡ ያልተገነዘበው የደርግ አገዛዝ ከዚህም ከዚያም በተከፈተበት ጦርነት በመደናበሩ የተነሳ ሳያውቀው በጀብደኝነት የወሰዳቸው የማያስፈልጉ እርምጃዎች ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል። ያም ሆኖ በተወሰዱት ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እርምጃዎች የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሳሰረ የመጣበትና የመፍጠር ኃይሉንም በመጠቀም እራሱን እንዲያውቅ ዕድል እንዳገኘ የማይታበል ሀቅ ነው። በጊዜው የነበረውን እርስ በርሱ የሚጋጭ ሁኔታና አንዳንድ መሻሻሎች መካድና ምንም ዕድገት አልነበረም ብሎ ዘመቻ ማካሄድ የህብረተሰብን ዕድገት ታሪክ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን እልም ያለ ክህደት ነው። በተጨማሪም ለጥፋቱ ተጠያቂው ደርግ ብቻ ነው ብሎ የማይሆን ውንጀላ ማካሄድ የህብረተሰብአችንን ህሊናዊና ባህላዊ አወቃቀር አለመገንዘብ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዐይነቱ ጭፍን አመለካከት ሳይንሳዊ ውይይት እንዳናካሂድ መንገዱን ይዘጋል።

ኢትየጵያ በአብዮቱ ወቅት የግሎባል ኢኮኖሚና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከጣለባት የፀረ-ዕድገት ማነቆ ቀስ በቀስ እየተላቀቀች ብትመጣም ይህ ሁኔታ የማርክሲዝምን ካባ ለብሶ በመጣ ኃይል እንዲቀለበስና ዛሬ አገራችን በግሎባል ኢኮኖሚ መዳፍ ስር እንድትዳሽቅ መንገዱን አመቻችቶ ሰጥቷል። ኤህአዴግ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እየታገዘ ስልጣን ከያዘ በኋላ ከአይ ኤም ኤፍና ከዓለም ባንክ ጋር በመስማማት የወሰዳቸው የኒዎ ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ኢትዮጵያ ግሎባላይዜሽን ወስጥ ገብታ ብቃትነቷን እንድታሳይ ሳይሆን፣ ግሎባላይዜሽን ኢትዮጵያ ውስጥ በመግባት (globalization is in Ethiopia, Ethiopia is not in the global economic order)የኢትዮጵያን ህዝቦች የወደፊት ዕድል በራሱ ፍላጎት ተወስኖ እንዲቀር የተወጠነ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው። ከዚህ በፊት በሰፊው እንደተተነተነው በገበያ ኢኮኖሚ ስም ተግባራዊ እየሆነ የመጣው ፖሊሲ ከውስጥ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ ማገዱ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ጥገኝነት በማጠንከር ይህንን የሚያራምድ የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ብሎ እንዲወጣና የግሎባላይዜሽን ተጠቃሚ በመሆን አስተሳሰቡንና ፍላጎቱን ከውጭ ኃይሎች ጋር በማቆላለፍ ወይም አሽከር በመሆን የአገራችን ሀብት በአሜሪካን ኢንቬስትሜንት ባንኮች ቁጥጥር ስር በማዋል ከፍትኛ ምዝበራ እንዲካሄድ ሁኔታውን እያመቻቸ ለመሆኑ ሁኔታውን ለሚከታተል ግልጽ ነው። በህንፃ ስራዎች በመሰማራት፣ ለአግሮ ዲዝል እርሻ መሬት በመከራየትና ገበሬውን ወደ ባርነት ስራ መቀየርና አገሪቱን ቀስ በቀስ በግሎባላይዜሽን መዳፍ ስር ማዋል ዕውነተኛ ሀብት እንዳይፈጠር መንገድ መዝጋቱ ብቻ ሳይሆን ባለው ሁኔታ መንፈሱ በመዳከምና በመረበሽ ወደ አልባሌ ቦታዎች የሚሰማራው የህብረተሰብ ክፍል እየበዛ በመምጣት ለማንኛውም አገዛዝ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር ከአሁኑ መተንበይ ይቻላል።

በአሁኑ ወቅት በአገራችን በነፃ ገበያ ፍልስፍና መሰረት የተቋቋመው የእህል ገበያ(commodity market) የዚህ የተወሳሰበ የግሎባላይዜሽን ሂደት አንድ አካል ሲሆን ያለውን የእህል እጥረትና የዋጋ ውድነት የሚያባብስ እንጂ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። የኮሞዲቲው ማርኬት ውስጥ ኢንቬስተሮች ይካፈላሉ። እነዚህ ኢንቬስተሮች ደግሞ የበለጠ ትርፍ እንዲገኝ የግዴታ ግፊት ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ የግዴታ የእህል ዋጋ እንዲወደድ በማድረግ የህብረተሰቡን የመግዛትና የመጠቀም ኃይል በማዳከም ወደ ድብቅ ረሃብ ውስጥ ይከቱታል ማለት ነው። ወይዘሪቱ ከአሜሪካ ቀድታ ያመጣችው የኒዎ ሊበራል የገበያ ልውውጥ ዘዴ ያልታቀደ ቀውስ እንደሚያመጣ ከአሁኑ መገመት ይቻላል። በተጨማሪም በሚፈጠረው ጤናማ ያልሆነ ወድድር ገበሬዎች የግዴታ ከዓለም አቀፍ የዘር አምራች ኩባንያዎች ዘር እንዲገዙና በማዳበሪያና በተባይ ማጥፊያ እየታገዙ እንዲያርሱ ይገደዳሉ። በዚህም የዓለም አቀፍ የእህል ዘር ኩባንያዎች በአገራችን ላይ በጂን የተዳቀለ ዘር(genetically modified seeds) ለማፍሰስና ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣውን የአገራችን የዘር ዐይነት እንዲወድም መንገዱ ይከፈትላቸዋለ። ገበሬዎችም የግዴታ የብድር ወጥመድ ውስጥ በመግባት ሊወጡ የማይችሉበት ሁኔታ ይወድቃሉ። ይህም ህብረተሰብአዊ ቀውስ ያስከትላል። በህንድ ዐይነት የታየው ቀውስና የአሜሪካን ኩባንያዎች መንገዱ ተከፍቶላቸው የህንድን ገበሬ መቆጣጠር እንደቻሉትና ለብዙ መቶ ሺህ ገበሬ ራስን መግደል ምክንያት እንደሆኑ ሁሉ የአገራችንም ገበሬ የዚህ ዕጣ ቀማሽ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ በአንድ በኩል ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የሚስማማና የሰውን ጤንነት የማያቃውስ ያስተራረስ ስልት ማዳበር ሲያሰፈልግ ለገበሬው በመንግስት የተደነገገና የገበሬውን ፍላጎት የሚያሟላ ዋጋ በመስጠት መንግስት ብዙ ትርፍ እህል በሚመረትበት ጊዜ ገዝቶ በማከማቸትና የእህል እጥረት በሚኖርበት ጊዜ በመሸጥ በየጊዜው የሚከሰተውን የእህል እጥረት መቋቋም ይቻላል። በተጨማሪም በየአካባቢዎች የተለያዩ ሰብሎችን ማረስ ለምርታማነት ዐይነተኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ ሲያስፈልግ በየቦታው ዲሞክራሲያዊ ኢንስቲቱሽኖች መቋቋም ለእርሻም ሆነ ለጠቅላላው የህብረተሰብ ዕድገት መሰረታዊና አስፈላጊ እንደሆኑ መታወቅ አለበት።  በዚህ መልክ ብቻ ግሎባላይዜሽን ከጣለብን ሸክም በከፊልም ቢሆን ልንላቀቅ እንችላለን። ይህንን ህልም ዕውን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ አገር ወዳዶች ተባብረው አንድ ነፃና ለህዝቦቿና ለመጭው ትውልድ አለኝታ ለመሆን የምትበቃ አገር ለመመስረት በአንድ ዓላማ ስር ካልተንቀሳቀሱ የህዝባችን ዕድል መሰደድና ለዘለዓለም ተዋርዶ መቅረት ዕጣው ይሆናል ማለት ነው።

ፈቃዱ በቀለ

ጽሁፉን ለመተቸትም ሆነ የተሻለ አስተያየት ለመስጠት ጸሀፊው ማንኛውንም ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ይጋብዛል። በአስተሳሰባችን እንድንዳብር ከተፈለገ ትችት ዐይነተኛ መሳሪያ ነው። ስለዚህ ጸሀፊው ከየአቅጣቻው የሚሰነዘረውን ትችት እንደነቀፌታ የሚመለከት ሳይሆን ሃሳብን ማዳበሪያ አድርጎ በመውሰድ በይዘትም ሆነ በጥራት የበለጠ ለማቅረብ ይረዳኛል ብሎ ያምናል። ካስፈለገም አጥጋቢ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነው። ስለዚህም አስተያየት ያላችሁ ሁሉ በሚቀጥለው አድራሻ ወይም በድህረ-ገጽ በመጠቀም አስተምሮ መማር የሚለውን መፈክር በመጠቀም ሰፋ ላለ ውይይት አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። አንድ ህብረተሰብ በሳይንሳዊ ትችት ብቻ ነው ዕድገት ሊያመጣ የሚችለው።ህብረተሰብአዊ ትችት የማይካሄድበት አገር ዕውነተኛ የስልጣኔን ብርሃን የማየት ዕድሉ የመነመነ ነው። የኢሜይል አድራሻ: fekadubekele@gmx.de