[gtranslate]

ሀቁን መናገር ወይስ ሀቁን ለመፈለግ መጣር ! ክፍል አንድና ኡለት!

                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   

       መግቢያ

 

       ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማርያም በተከታታይ ባወጣቸው አምስት ጽሁፎቹ በተለይም በፖለቲካ ትግል ውስጥ የምንሳተፈውን ከባድ ፈተና ውስጥ እንደጣለን የማይካድ ነው። በነዚህ አምስት ጽሁፎቹ ብቻ ሳይሆን በተለይም ባለፈው አንድ ዐመት ሳያቋርጥ የሚያወጣቸው ጽሁፎች የሚያስመሰግኑት ናቸው። ፕሮፌሰር አልማርያም ምርታማ ጸሀፊ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ መሆኑን በግንባር ቀደምትነት በመቆም የሚታገል መሆኑን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ህያው ምስክር ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ አቀራረቡ ዘመናዊና አጠር መጠን ብሎ ብዙ ቁም ነገሮችን አዝሎ የሚወጣ ጽሁፍ በመሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን እንድናቀርብ ወይንም ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚገፋፋንና ወደ ቁም ነገሮች ላይ እንድናተኩር የሚጋብዘን ትምህርታዊ ጽሁፍ ነው።

       እንደዚህ ዐይነቱ ጽሁፍ አልፎ አልፎ በአማርኛ ቢቀርብ ብዙ አንባቢያንን ከማዳረሱም ባሻገር ለአማርኛ ቋንቋችን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማበርከት በበቃ ነበር። እንደሚታወቀው የማንኛውም አገር ምሁር ማንኛውንም ጽሁፍ በአገሩ ቋንቋ ጽፎ ቢያቀርብ ብዙ አንባቢ ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰብአዊ፣ ለኢኮኖሚ፣ ለባህልና ለተፈጥሮ ሳይንስ ዕድገት የሚያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ማንኛውም ህብረተሰብ በአደገበት ቋንቋ ቢማር፣ ቢጽፍና ሃሳብ ለሃሳብ ቢለዋወጥ የበለጠ ለመግባባት መቻሉ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጥንካሬን በማግኘት አስተሳሰቡ ጠለቅ ያለና የሰፋ ይሆናል። ይህንን የምለው ካለምክንያት አይደለም። በብዙ የኢትዮጵያ ድህረ-ገጾች ላይ ከአማርኛ ቋንቋ ይልቅ በእንግሊዘኛ መጻፉ እየተለመደና ቋንቋችንን እየገፋው በመምጣቱ የኤሊቲሲዝም ሰሜት እየዳበረ ነው።  በዚህ ከቀጠለ ሁኔታው ለከፋፋዮች የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን ለዕድገት የሚደረገውም ርብርቦሽ አቅጣጫውን እየሳተና ጊዜውም እየረዘመ ይሄዳል። እንደዚህ ዐይነቱ በራስ ቋንቋ አለመናገርና አለመጻፍ በአስራስምንተኛውና በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን በጀርመንና በራሺያም ከፍተኛ ችግር አስከትሎ እንደነበር ይታወቃል። ፈረንሳይኛ የነገስታቱና የመሳፍንቱ መነጋገሪያና መዳሪያ ቋንቋ ነበር። በዚህም ምክንያት በሰፊው ህብረተሰብና በአገዛዙ መሀከል መግባባት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም አገሮች በሊትሬቸርም ሆነ በሳይንስ እንዲሁም በባህል ለማደግ ያላቸው ኃይል ውስን ነበር። በጀርመን የራስን ቋንቋ ማዳበር አስፈላጊነት የተረዱት እንደ ሜንደልሰን፣ ሌሲንግና ሺለር የመሳሰሉት ፈላስፋዎች፣ የድራማና የሊትሬቸር ተመራማሪዎችና ጸሀፊዎች የጀርመንኛ ቋንቋ እንዲዳብርና የፈረንሳይኛ ቋንቋ ደግሞ ተገፍቶ እንዲወጣ ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ። በራሽያ ደግሞ ታላቁ ፑሽኪን ሊትሬቸርንና ግጥምን በራሸያ ቋንቋ እየጻፈ በማቅረብ አገዛዙን ይጋፈጣል። ቀስ በቀስም ራሸያንኛ በምሁሩ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረውና መሰረት እንዲይዝ በማድረግ ለሊትሬቸር መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ስለሆነም ተከታታዩ የራሺያ ምሁር ፑሽኪንን የራሺያ ቋንቋ ከባድ ፈተና ውስጥ በወደቀበት ወቅት እግዚአብሄር ከሰማይ የወረወረው ሊቅ ነው ብሎ ይጠራዋል። በእርግጥም በሁለቱም አገሮች ህብረተሰብአዊ ዕድገት ሊታይ የቻለው ቋንቋችው መዳበር ከጀመረ ወዲህ ነው። ጀርመን የአሳቢዎችና የገጣሚዎች አገር ተብላ መጠራት የጀመረችውና የተለያዩ የፍልስፍና ፈለጎች መዳበር የጀመሩት የጀርመን ቋንቋ መስፋፋት ከጀመረና እንደመመሪያ ተቀባይነት ካገኘ ወዲህ ነው። የሁለቱን አገሮች የዕድገት አቅጣጫ ልዩነትና ምክንያት ወደ ጎን ትተን በራስ ቋንቋ መነጋገርና መጻፍ የሰውን የማሰብ ኃይል እንደሚያበለጽግና አርቅቆም ለማሰብ እንደሚረዳ በቋንቋ ተመራማሪዎች የተደረሰበት ውጤት ነው። እያንዳንዱ ምሁር የራሱን ቋንቋ ለማዳበር የሞራልና የታሪክ ግዴታ አለበት። ካለራስ ቋንቋ መዳበር በፍጹም ዕውነተኛ ዕድገትና በሁሉም አቅጣጫ ሊገለጽና ሊታይ የሚችል ስልጣኔ ሊኖር አይችልም።

       እዚህ ላይ ይህንን ጉዳይ አጥብቄ የማነሳው ፕሮፌሰር አለማየሁን ለመተቸት አይደለም። እኔም እንደሱ ከተፈቀደልኝ ሀቁን ለመናገር ፈልጌ ነው። ፕሮፌሰሩም ሆነ ሌሎች ለምን በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደሚጽፉ ችግሩ ይገባኛል። ብዙዎቻችን ከአገራችን ተራርቀን ስንኖር ዘመናት አሳልፈናል። ብዙዎቻችን የምናነበው ስነ-ጽሁፍ አይ በእንግሊዘኛ ወይም ባለንበት አገር ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፎችንና ጋዜጦችን ወይም መጽሄቶችን ነው። በጥሩ ቋንቋ የተጻፉ የአማርኛ ስነ-ጽሁፎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የተጻፉም ወይም የሚጻፉ ካሉ ሳይንሳዊና ታሪካዊ አቀራረባቸው ስነ-ጽሁፍ የሚያሰኛቸው አይደሉም። የህብረተሰብአችንን የማቴሪያልና የመንፈስ እንዲሁም የስነ-ልቦና ሁኔታ ጥበባዊ በሆነ መልክ ማቅረብ የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። እንደ ጎተ፣ ሺለረ፣ ሌሲንግና ሜንደለሰን የመሳሰሉ የድራማና የሊትሬችር ምሁሮች፣ በፍልስፍና ደግሞ እንደ ላይብኒዝ፣ ካንትና ሄገል እንዲሁም ኒትቸን የመሳሰሉትን ፈለግ የሚከተሉ ጸሀፊዎች በአገራችን ምድር አልተፈጠሩም። እንድነ ፍቅር እስከመቃብርንና አርአያን እንዲሁም የብርሃኑ ዘሪሁንን የመሳሳሉትና የህብረተሰብ ትችት የተገለጸባቸውን አቀራረቦች ተከትሎ የሚጽፍ ትውልድ ብቅ ለማለት ባለመቻሉ የአዲሱ ትውልድ የአጻጻፍ ስልት ከህብረተሰቡ የአኗኗርና ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ እየራቀ የመጣ በመሆኑ ለስነ-ጽሁፍና ለቋንቋ ዕድገት ያለው አስተዋጽዖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሚጻፉት ጽሁፎች „በቀጥታ በምናያቸው“ ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው ወደ ውስጥ ገብተን የነገሮችን ምንነትና ዕድገት እንዳንረዳና እንዳንመረምር እንቅፋት ሊሆኑ ችለዋል ብል እንደ ውንጀላ አይቆጠርብኝም። ስለዚህም እንድነ ሺለርና ሌሲንግ እንዲሁም እንደነ ሼሊ የመሳሰሉትን የድራማና የግጥም ሊቆች ፈለግ ተከትለን ህብረተሰባችንን መቃኘትና መግለጽ እስካልቻልን ድረስ ስልጣኔን የመጎናጸፉ ተስፋ እየመነመነ ይሄዳል ማለት ነው።

       በራስ ቋንቋ የመጻፍን አስፈላጊነት ካነሳሁ በኋላ የማቀርበው ጥያቄ እስካሁን የፕሮፌሰር ሃይለማርያምን ጽሁፍ እንደተከታተልኩት፣ በእርግጥም በግልጽ የምናየውን ነገር ግን ደግሞ አንዳንዶቻችን ይህን ያህልም ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባነውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሰቀምጥ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በሳይንስ ዓለም ውስጥ ሁለት ሰዎች አንድን ነገር በተለያየ የሳይንስ መነጽር ይመለከቱታል። አንደኛው ምናልባት በሰው የተሰራን የተወዛገበ ሁኔታና መንፈሳዊ ቀውስ እንደተፈጥሮአዊ ሁኔታ አድርጎት ሊወስድ ይችላል። ሌላኛው ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ በአንድ አገር ውስጥ በሚገኝ የህብረተሰብ አወቃቀርና ሀብትንና ስልጣንን በሚቆጣጠር ኃይል ሆን ተብሎ ወይም ሳይታሰብ የሚፈጠር ሁኔታ አድርጎ በመውሰድ የሁኔታውን የግዴታ መለወጥ ያመለክታል። ሌላው ከዚህ ለየት አደርጎ የሚመለከተው ደግሞ የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ህብረተሰብአዊ ድህነትና የአስተዳደር ብልሹነትና፣ አንድ አገር ጥበባዊ ሆኖ አለመደራጀት በተጨባጭ ከሚታየው ሁኔታ በሻገር መገለጽና መተንተን እንዳለበት ያመለክታል። በሌላ አነጋገር በሁለት ወይም በሶስት ምሁርች ዘንድ የአንድን ህብረተሰብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ሁኔታ ለመመርመር የምርመራው ዘዴ ይለያያል ማለት ነው። ስለሆነም አንድ ጸሀፊ ስለአንድ ሁኔታ ሀተታ ሲሰጥ በምን ዐይነት የሳይንስ መነጽር እንደሚመለከትና እንደሚመረምር ከአቀራረቡ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም በአጠቃላይ ሲታይ አንባቢያን የፕሮፌሰር ሃይለማርያምን ትንተና ከኤስቴቲካዊ አቀራረቡ ባሻገር እንዴት እንደሚመለከቱት ቢነግሩን ደስ ይለኛል። ከዚህ ስነሳ ጥያቄ የማቅረብና የአስራር ስልት የሚባል 㜎የአጻጻፍ ዘዴ አለ።

ጥያቄ የመጠየቅና የአሰራር ስልት ጉዳይ!

       ማንኛውም ህብረተሰብን ወይም ሳይንስን የሚመለከት ጽሁፍ እንዲሁ ለመጻፍ ተብሎ አይጻፍም። በሌላ ወገን ደግሞ ዝም ብሎ እንደልማድ ወይም እንደ አስፈላጊነት ብቻ የሚታይ ብዙም ጥያቄ ለመጠየቅ የማያስገድድ ሁኔታ አለ። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው አንድን ነገር እንደተፈጥሮአዊ አድርጎ ስለሚወስደው ካለብዙ ጭንቀት ሳያወጣ ሳያወርድ ይኖራል። ለምሳሌ የሰው ልጅም ሆነ እንስሳ እንዲሁም ተፈጥሮ ካለ ውሃ መኖር አይችሉም። ውሃ ለሰው ልጅ መኖር የግዴታ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ማንም ቢሆን ውሃ እንዴት እንደሚፈጠር ወይም በተወሰነ ኬሚካል ሬአክሽን ለምንስ በኦክስጅንና በሃይድሮጅን ውህደት ብቻ መፈጠር እንደሚችል እስከዚህም የሚያወጣ የሚያወርድ የለም። ውሃ ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ፍጥረት ለሚባል ነገር ሁሉ የግዴታ እስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበን እንዳይባክንና በጥንቃቄም መያዝ እንዳለበት ሃላፊነት በተሞላው አስተሳሰብ የምንጠቀም እስከዚህም ብዙዎቻችን አይደለንም። ሲጠማን ብቻ ወይም ምግብ ለማብሰልም ሆነ ለማጠብ ሲያስፈልገን የዚያን ጊዜ መንደፋደፍ እንጀምራልን። ውሃ ባይኖር ኖሮ ወይም ደግሞ ውሃ በአንድ ጊዜ ቢጠፋ ምን እንሆናለን ብለን ራሳችንን የምንጠይቅ እስከዚህም ብዙ አይደለንም። የውሃ ተመራማሪና ለውሃ በአንድ አካባቢ እንደልብ መገኘት ከብዙ ነገሮች ጋር የተያያዘና የውሃ መጠንም ዝቅ እንዳይል በየጊዜው መወሰድ ያለበትን እርምጃ የሚከታተል ኢንስቲቱሽና ተመራማሪ እስከሌለ ድረስ አንድ ቦታ ላይ ቆም ብሎ ለማሰብ በማይቻልበት ህብረተሰብ ውስጥ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ውሃ እጥረትና ለህዝብም እልቂት ምክንያት ሊሆን የሚችል ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህም ውሃ አስፈላጊ መሆኑን መረዳቱ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ህብረተሰብ በውሃ እጥረት እንዳይሰቃይ በየጊዜው በቂ ምርምርና እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል። ለውሃ እጥረት፣ መባከንና ለዝናብ እጦት ምክንያት የሆኑ ህብረተሰብአዊ ምክንያቶችንና ሰው ሰራሽና በአየር መበላሸት ምክንያት  የሚከሰቱ ችግሮችን እየመላለሱ መጠየቅ ችግሩ እንዲገታ ወይም እንዳይባባስ እርምጃ መውሰድ ያስችላል። እንደዚህ ዐይነት ምርምርና ግንዛቤ ሊኖር የሚችለው ህብረተሰብአዊና ተፈጥሮን የመንከባከብ ኃላፊነት እንደባህልና የሞራል ግዴታ ተደርጎ በሚወሰድበት ህብረተሰብ ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ በራሱ ስለሰው ልጅ ምንነት መረዳትና የተማረው ደግሞ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት እንዳለበት የተገነዘበ የተማረ የህብረተሰብ ክፍል ባለበትና ለአንድ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱም ዜጋ ኃላፊነት የሚሰማው የነቃ የምሁር ኃይል ካለ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአጠቃላይ ሲታይ ለማንኛውም ህብረተሰብአዊ ችግር ጥያቄ ለማቅረብና መፍትሄ ለመሻት የግዴታ ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ንቃታ-ህሊና ያስፈልጋል። በዘልማድ ከሚሰሩና በቀጥታ በምናያቸው ነገሮች ላይ ብቻ ከመመካት ይልቅ ንቃተ-ህሊናችንን ብናስቀድምና የአንድን ነገር መነሻና ሂደት ለመረዳት ጥያቄዎች እየመላለስን ብናቀርብ ስህተትን ከመስራት ልነቆጠብ እንችላለን። ጉዳትም እንዳይደርስ ከመጀመሪያውኑ መከላከያ ማዘጋጀት ይቻላል። ለጊዜው ከቁጥጥር ቢወጣ እንኳ አስፈላጊው ዝግጅትና በቂ መሳሪያዎች ካሉን ችግሩን በፍጥነት መቋቋም እንችላለን። ዛሬ የምናያቸው፣ የምንጠቀምባቸውና የምንደላቀቅባቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች ትላንት ወይም ዛሬ የተፈጠሩ ሳይሆኑ የብዙ ሺህ ዐመታት የቀስ በቀስ ምርምሮችና ፈጠራዎች እንዲሁም ወደ ተግባርነት የተመነዘሩ ናቸው። የተወሰኑ የአሰራር ስልቶችና የጥያቄ አቀራረብ ዘዴዎች ውጤቶች ናቸው።

       ፕሮፌሰር ሃይለማርያምና ሌሎች በየጊዜው ወደሚያነሱትና ወደሚተነትኑት ተጨባጩ ሁኔታ ልምጣ። ለምሳሌ ስለ ወያኔ አምባገነናዊነት፣ መግደል፣ ስለ ህግ የበላይነት አለመኖር፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ እንደሚጻፈው ከሆነ ስለ አገዛዙ አርቆ አለማሰብ ወይም ድንቁርና እንዲሁም ዲሞክራሲያዊው የዓለም ማህብረሰብ/የምዕራቡ ዓለም በአቶ መለስ ብልጣ ብልጥነት መታለሉና ሁኔታው ትክክል መስሎት ርዳታ እንደሚለግስ … ወዘተ. ይጻፋል። ጭፍን ያለ የወያኔ ደጋፊ ካልሆነና ዛሬ ባለው ሁኔታ መጠቀም አለብኝ ብሎ ለመብላት ከሚፘፘጠው ጊዜው ያበቀለው አራዳ በስተቀር እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ለሁላችንም በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ብዙም ሀታታ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። አገዛዙ አምባገነን ስለሆነ በጭፍን ሰውን ይገድላል! ከሃዲ ስለሆነ መሬት ለውጭ ከበርቴዎች ይሸበሽባል! ለራሱ ብቻ ስለሚያስብ ሰፊው ህዝብ ይራበው አይራበው ጉዳዩ አይደለም! ነጥብ ! እንደዚህ እያልን ካለብዙ ሀተታና ጭንቀት ማሰቀመጥ ይቻላል። ብዙ ጊዜና ቦታ መፍጀት ባላስፈለገ ነበር። እንደዚህ ብለን አጠር መጠን አድርገን ካስቀመጥን ደግሞ፣ እንደዝንባሊያችን መልሳችንም አይ አገዛዙን በአመጽ መጣል ወይም ደግሞ የእግዚአብሄር ቁጣ ስለሆነ ጊዜ እስኪፈታው ድረስ ዝም ብሎ መቀመጥ ነው የሚል ይሆናል።

       የዛሬውን አገዛዝ ድርጊት ከላይ እንደተቀመጠው የመረዳቱ ላይ አይደለም ችግሩ። ወይም ደንቆሮ እያልን ስለተናገርን ከድንቁርናው ሊታገስና ወደ ቀና መንገድ ሊመጣ የሚችል አገዛዝ አይሆንም። እንዲያውም፣ እኔ ሳልሆን ደንቆሮው እናንተው ናችሁ፤ እኔማ ብልጣ ብልጥ በመሆኔ  ከምዕራቡ ዓለም ጋር እየተዳራሁ ስራዬን እየሰራሁ ነኝ ይላል። አገር ማስታዳደር ይህ ነው፤ ከዚህ በላይ ሌላ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ከቶ ሊኖር አይችልም ብሎ እቅጩን ይነግረናል። ለሱ የሚታየው ምናልባት ለኛ „አይታየንም“ ይሆናል። እኛም እሱ የሚያደርገው እንደማይገባን ሁሉ፣ ወይም ደግሞ እየገለጽን ግን ጠለቅ ብለን በመሄድ የችግሩን መነሻና እየተወሳሰበ መምጣት ከብዙ ሁኔታዎች ጋር ለማያያዝ አለመቻል እንደሚያሰቸግረን ሁሉ እሱም እኛ የምንለውን ሊረዳው አይችልም ይሆናል።

       ስለዚህም ስለዛሬው አገዛዝ አምባገነናዊነትና ከምዕራቡ ዓለም ስለሚያገኘው ርዳታና የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ስላለው እርካታ ምናልባት በክስተት ደረጃ ብንስማማም ጠለቅ ብለን ጥያቄን በጥያቄ እያነሳን ስንሄድ ብዙ የማያገናኙን መንገዶች አሉ። እንደ አደግንበት፣ እንደተማርነው የትምህርት ዐይነትና አቀሳሰም፣ እንዳለን የማህበራዊና ኢከኖሚያዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም ደግሞ እንደምንኖርበት አካባቢ አንድን ነገር የመረዳትና መፍትሄ የመስጠቱ ጉዳይ በአስተሳሰብ እንለያያለን። ስለ አንድ ሁኔታ ዕድገትና ሂደት የሚኖረን ግንዛቤና ያንን በጽሁፍ አቅርቦ ለሰው ለማስረዳትና ደጋፊም ለማግኘትና  ለማሳመን የምንጥረው አንድ በጭንቅላታችን ውስጥ በቀረጽነውና እንደ „ሳይንሳዊ“ የመተንተኛ ዘዴ አድርገን በወሰድነው ስልት ብቻ ነው። በየጊዜውም በአዳዲስ እርእስቶች ላይ ስንጽፍ እየደጋገምን ሳናውቅ በዚህ ዐይነቱ የአጻጻፍ ስልት እንሽከረከራልን። ይሁንና የምንጠቀምበት የአጻጻፍ ዘዴ የቱን ያህል ተጨባጭ ሁኔታውን ያንጸባርቅ አያንጸባርቅ፣ የህብረተሰባችንን ችግር መተንተኑ ብቻ ሳይሆን መፍትሄም ይጠቁማል ብለን ጥብቅ የአስራር ስልትን ተከትለን የምንጽፍ ሁላችንም አይደለንም። አንድ ቦታ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ አንድ ግለሰብ ስለ አንድ ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ወይም አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ችግር ለመጻፍ በሚነሳበት ጊዜ እንደተራ የጋዜጣ አቀራረብ መመልከት የለበትም። ጋዜጠኛ አንድን ሁኔታ ባይተዋር በሆነ መልክ የችግሩን መነሻ በጥልቅ ሳይመረምር ለማቅረብ ይጥራል። እንደዚህ ዐይነቱ አቀራረብ ዜና እንደመሆኑ መጠን ከሳይንሳዊ አሰራር ስልት አንጻር ሲመረመር ሳይንሳዊ አይደለም። አንድ ጋዜጠኛ ጥያቄን በጥያቄ በማቅረብና ትክክል ነው ብሎ የሚያምንበትን የአሰራር ዘዴ በመከተል የሚጽፍ ሳይሆን፣ ከዚህም ከዚያም በመለቃቀም ወይም በአርቺቭ ውስጥ የተጠራቀመቱን በመመርመር ለአንባቢያን የሚያቀርብ ነው። የህብረተሰብ ችግር ይመለከተናል የምንል እንደኛ ያለው ጸሀፊ ግን 㗹አጠር መጠን ያለችም አርቲክል ሊጽፍ ሲነሳ ከጋዜጠኛ ለየት ባለ መልክ ለማቅረብ መጣር አለብት። ለምሳሌ አንድ ጸሀፊ ስለ አገራችን የኢኮኖሚ ችግርም ሆነ አገዛዙ እንደሚለን ስለ ዕድገት ሲጽፍ የሚነሳበት የአሰራር ዘዴና ርዕይ አለ። ዝም ብሎ ግን እከሌ እከሌ እንደዚህ አለ ብሎ አንዱን እየጠቀሰና ስለ አገራችን „የኢኮኖሚ  ሁኔታ“ ቢጽፍ አቀራረቡ ከጋዜጠኛ አቀራረብ በምንም አይለይም።

       በመሆኑም ስለ ወያኔ አገዛዝና በምዕራቡ መሀከል ስላለው የእከክልህ እከክልኝ ግኑኝነት ስንጽፍ፣ አገዛዙና የምዕራቡ ዓለም ለማሳመን እንደሚሞክሩት ከነሱ ፖሊሲ በስተቀር ሌላ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄን ሊያመጣ የሚችል ሌላ መንገድ የለም ወይ? የምዕራቡ ዓለም መረጋጋት ሲልስ ምን ማለቱ ነው? ከዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ዕድገት አንጻር ሲመረመር መረጋጋት የሚሉት ጽንሰ-ሃሳብ እውነትም ሳይንሳዊ ይዘት አለው ወይ? መረጋጋት ሲሉስ በእርግጥስ ለኢትዮጵያ ህዝብ አስበው ነው ወይ? ለምንስ ወያኔን የሙጥኝ ብለው ይዘው ካላንተ አማራጭ የለም እያሉት በቢሊዮኖች የሚቆጠር „ርዳታ“ ያፈሱለታል? በአጠቃላይ ሲታይ ለምንድነው አምባገነኖችን የሚደግፉት? በሌላ ወገን ደግሞ ለምንድነው እንደ ኢራንና የዚምባዌን አገዛዝ ላይ „አደገኞች“  ናቸው እያሉ ዘመቻ የሚያካሂዱት? ለምንድነው እኛስ እባካችሁን አትርዱ እያልን የምንማጸነው? በእርግጥስ ሞራልና ስነ-ምግባር አላቸው ብለን በማመንና በመገመት? ወይስ አቅመ-ቢሶች በመሆናችን? ወይስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዋቀረው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሚሊታሪያዊ ቅንብር ይህ ብቻ ነው ብለን ስለምናምንና በዚያው ውስጥ የግዴታ ገብተን ከመንደፋደፍ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም ብለን ጭፍን ብለን ስለተቀበልን? ስለሆነም ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋውን የኢኮኖሚ አወቃቀር በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ነው፤ በመሆኑም ብዝበዛና ህዝቦችን ማፈናቀል እንዲሁም አካባቢን ማቆሸሽና ማውደም፣ የጥሬ-ሀብት ዘረፋ እያካሄዱ የአንድ አገር ህዝብ መኖሪያ እንዲያጣ ማድረጉ የስርዓቱ ወስጣዊ ባህርይ አይደሉም ብለን ስለምናምን?  በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዋቀረው የአገዛዝ ሰንሰለት በተወሰነ ሎጂክ ሳይሆን፣ ሁሉም አገር ነጻነቱን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ መሆኑን በመገንዘባችን?  አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል እንደኛ አገር ያለውን አገዛዝ አባልጎ በአገራችን ስልጣኔ እንዳይመጣና ህዛባችንም ነፃነት እንዳይቀዳጅ የሚሰራው ደባ የለም ብለን በማመናችን?  የኛ የፖለቲካ አመለካከትና የትግል ስልት ከላይ የቀረቡትን ጥቄዎች መሰረት ካደረገ፣ እንዴትስ አድርገን ከህዝባችን ጎን መሰለፍ እንችላለን? እንደዚህ ብለን ካመን ደግሞ በእርግጥስ ጠቅላላው ሰለጠንኩኝ የሚለው የምዕራቡ ዓለም ከጎናችን ሊሰለፍ ይችላል ወይ? ከኛና ከወያኔ ማንን ይመርጣል ብለን እንገምታለን? ብዙ መነሳትና መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች !

ሶስት የጥያቄ አቀራረብና የምርመራ አጻጻፍ መንገዶች !

               ከፕሬ-ሶክራተስ በፊት የነበረውን ተፈጥሮን የመመርመሩንና በዚህ ዓለም ላይ የሰውን ልጅ ሚና ለመረዳት ጥያቄ የማቅረቡን ጉዳይ ወደ ጎን ትተን በአጠቃላይ የግሪክ ፈላስፎች ከጥንታዊ አምልኮት(Mythology) አስተሳሰብ ተላቀው የሰውን ልጅ ሚና ሲጠይቁ የደረሱበት ድምደማ በጊዜው ለነበረው ጭቆናም ሆነ ድንቁርና፣ እንዲያም ሲል የወንድማማቾች ርስ በርስ መጨፋጨፍ ተጠያቂ አምላኮች ሳይሆኑ ራሱ የሰው ልጅ እንደነበር ነው። ስለሆነም በዚያን ጊዜ የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታና የሰውን አስተሳሰብ ለመመርመር ሶክራተስ የደረሰበት፣ 1ኛ)ዕውነተኛውን መንገድ መፈለግና ዕውነተኛውን ደስታ ለመጎናጸፍ መንፈስን በየጊዜው ማደስ እንደሚያስፈልግ፣ 2ኛ) ዕውነቱንም የመፈለጉ ጉዳይ እየመላለሱ ራስን በመጠየቅ ላይ ያተኮረ( by means of Logos, i.e. reason)፤ ስለሆነም በምንም ዐይነት ከውጭ በሰፊው ህዝብ የሚነገርንና የሚነዛን አስተሳሰብ ወይም በአንድ ማዕከላዊ ኃይል የሚነገርን በምርምር ላይ ያልተመሰረተን ወሬ አለመቀበል፣ 3ኛ) ይህንንም ሀቁን የመፈለግ ምርምር በሞት ትቀጣለህ ቢሉ እንኳ በፍርሃቻ ተውጦ ውሸትን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን፤ እንዲያውም የውሸት ተገዢ ሆኖ ከመኖር ይልቅ ለዕውነት መሞትን መምረጥና ጥቅሙንም መረዳት፣ 4ኛ)ሀቁንም የመፈለጉ ጉዳይ ከውስጥ መምጣት እንዳለበትና፣ ይሁንና ፍጹማዊ ዕውነት ለማግኘት እንደማይቻልና ወደዚያ የሚደረገውን ጉዞ አለመዘንጋት የመንፈስን ጥንካሬ ለማግኘት የማያቋርጥ ትግል ማድረግ።

       ይህ ዕውነትን የመፈለጉና የማግኘቱ ጉዳይ በቀጥታ በምናያቸው ነገሮች ላይ የተመረኮዘ አይደለም። የተደበቀና ስለዚህም ራስን በማስጨነቅ የተፈጥሮን ምስጢር እንድንረዳ የሚያሳየን ትክክለኛው መንገድና ራሳችንን አውቀን ራሳችንን እንድንለውጥና በሰው ልጅና በተፈጥሮ መሀከል መደጋገፍ እንዳለ የሚያስገነዝበን ዕውነቱን የመፈለጊያ ዘዴ ነው። የጥበቡና የሳይንሱ መንገድ ነው። የሰው ልጅ ከእንስሳ መለየቱን የሚያረጋግጥና በማሰብ ኃይሉ ብቻ አንድን ነገር በተለያየ መልክ መለወጥ እንደሚችል የሚያሳየን ነው። የመንፈስ ኃይል በቀጥታ ከምናያቸው ነገሮች የበለጠና የሚያድግ፣ ከተጨባጩ ነገርና(Matter)  የአላቂነት ባህርይ ካለው ጋር ሲወዳደር ዘላቂነት ያለውና ሊዳብርም ወይም ሊሰፋ የሚችል፣ በአስተሳሰባችን እየጎለበስን ስንሄድ የበለጠ የተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ምንነት እንድንረዳ የሚያስተምረን ፍልስፍናዊ ዘዴ ነው። ስለሆነም ይህ በመንፈስ ወይም በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመረኮዘው ዕውነትን የመፈለጉ መንገድ የዕውቀት መመርመሪያ መነሻና ዕውነተኛውን የነጻነት ፈለግ የሚያሳየን ነው።

       የሶክራተስን ዕውነትን የመፈለግ መንገድ እየተቀናቀነ የወጣው ሌላው „ዕውነትን የመፈለጉ“ ዘዴ ግን በቀጥታ በምናየው ላይ(Sense Perception) የተመረኮዘ ነው። ይህም የሶፊስቶቹ መንገድ ነው። ሶፊስቶች ሶክራተስን ይከሱ የነበረው ወጣቱን አምላኮች የሉም እያለ የሚያስተምር ነው በማለት ነበር። ስለሆነም ህግም ሆነ አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ስርዓት በአንድ በተዋቀረ አገዛዝ ከላይ ወደታች ለህዝብ የሚወረወር እንጂ እያንዳንዱ ግለሰብ ከዚህ ወጣ በማለት ራሱን በመጠየቅ ዕውነተኛውን ግለሰብአዊ ነጻነት ለማግኝት የሚችል አይደለም በማለት ነበር የሚሰብኩት። የፕላቶ ተማሪም የሆነው አርሰቲቶለስ ይህንንን የሶፊስቶችን መንገድ በመከተል መሬት የፕላኔቶች ሁሉ ማዕከላዊ እንደሆነችና፣ ሌሎች ፕላኔቶችና ፀሀይም ጭምር በሷ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው ብሎ በማሰተማሩና ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረጉ የግሪክ ስልጣኔ ከወደመ በኋላ ኮፐርኒከስ ብቅ ብሎ ይህንን አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን በምርምር ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የሳይንስ ዕድገት ሊቀጭ ችሏል። የካቶሊክም ሃይማኖት ይህንን የፖትሌሚየስና የአርስቲቶለስን የተሳሳተ አስተሳሳብ በመቀበልና በማስፋፋት የአውሮፓው ህዝብ በጨለማ ዘመን እንዲኖር ለማድረግ በቅቷል። የጨለማው ዘመን ግን ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ቢመጣም፣ ሙሉ በሙሉ ሊደመሰስ የቻለው ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ  በሬናሳንስ አማካይነት ነው። ይህ የሰብአዊነትንና የሰውን ልጅ የመፍጠር ችሎታና የበላይነት ያረጋገጠ ፍልስፍና ለስልጣኔ መሰረት እንዲጣል ካስቻለ በኋላና በብዙ የማዕከለኛው አውሮፓ አገሮች መሰረታዊ ለውጥ መንገድ ከከፈተ በኋላ፣ ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ግን መልኩን ለወጥ አድርጎ በመጣ አዲስ ኦሊጋርኪያዊ አስተሳሰብ ሊቀጭ ችሏል። የሰው ልጅ ዐይኑን እንዳይከፍትና ስልጣኔን እንዳይቀዳጅ በሩ ይዘጋበታል። ከዕውነተኛው ግለሰባዊነት ይልቅ በክስተት ላይ የተመሰረተ ሊበራሊዝም ወይም የህግ የበላይነት የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በማስፋፋት አዲስ ህብረተሰብአዊ ኃይልና በጥቂት ሰዎች ዘንድ ሀብት እንዲከማችና የሰውም ልጅ ዕድል በጥቂት ስልጣንን በጨበጡና ሀብት ባላቸው እንዲወሰን ያደርጋል። ዛሬ በዓለም ላይ የተንሰራፋው የሊበራሊዝም ርዕዮተ-ዓለምና የግሎባል ኢኮኖሚ ልቅ ማጣትና በጥቂት ሰዎች ዘንድ ተከማችቶ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች ተመጽዋች ሊሆኑ የበቁት የሶፊስቶች አመለካከት በረቀቀ መልክ በኤምፒሪሲዝም አማካይነት በትምህርትና በሌሎች ኢንስቲቱሽኖች ዘንድ በመስፋፋቱና ስር በመስደዱ ምክንያት ነው። ከፖለቲካ እስከ ህብረተሰብ ጥያቄና እስከ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ድረስ የዓለም ማህበረሰብ ይህንን የሶፊስቶችን ወይም የኤምፒሪሲስቶችን ፍልስፍና መከተልና ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ዛሬ እንደምናየው እንደ ሃይማኖት የተወሰደ ርዕዮተ-ዓለም ነው። የነፃ ንግድና የነፃ ገበያ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ ጥቅም ሲል ብቻ ነው የሚታገለው የሚለው የዩቲሊታሪያን ፅንሰ-ሃሳብ በዚህ በሶፊስቶች ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ነው።

       ሶስተኛውና ሀቁን የመፈለጉ መንገድ በማርክሲዝም ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ የሀብት ቁጥጥርንና ክፍፍልን መሰረት ያደረገ በቀጥታ ሊታይ የሚችል፣ ይሁንና ግን እንደ ተፈጥሮአዊ የሚወሰድ በቀላሉ በግንዛቤ ውስጥ ሊገባ የማይችል የምርምር ዘዴ ነው። የማርክሲዝም ፍልስፍና ኤፒኩሪያን በሚባሉ የግሪክ ማቴሪያሊስት ፈላስፋዎች አስተሳሰብ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን የመንፈስን ኃይል ሙሉ በሙሉ ሳይክድ የአንድ ህዝብ አመለካከትና አስተሳሰብ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በሚገኝ የማቴሪያልና የኃይል አሰላለፍ ሁኔታ ሊወሰን ይችላል ብሎ ያስተምራል፤ ያምናል። ስለዚህም በማርክስ ዕምነት አንድ ህብረተሰብ የተለያዩ መደቦች ተፋጠው የሚገኙበት ሲሆን የሚደረገውም ትግል ሀብትን በሚቆጣጠሩና በማይቆጣጠሩ መሀከል ነው። ሀብትን የሚቆጣጠረውና የዚህን መደብ ጥቅም የሚያስጠበቀው የመንግስት መኪና የገዢው መደብ የበላይነቱን ይዞ እንዲቆይ አንድ ህዝብ ንቃተ-ህሊናው እንዲላሽቅና የነገሮችን ምንነት ጠለቅ ብሎ እንዳይገነዘብ የርዕዮተ-ዓለም ሰበካ ያደርጋሉ። ስለዚህም ካፒታሊዝም ሁለንታዊ በመሆን ሰውነትን ተብዝባዠ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የሰው አስተሳሰብ አንድ አቅጣጫን በመያዝ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ዞር ብሎ እንዳይመለከትና እንዳያስብ ያደርጋል ይላል። ዋን ዳይሜንሽናል ማን እንደሚሉት አነጋገር ነው ማለት ነው። በማርክስና በማርክሲስቶች ዕምነት ከላይ የሰፈረው አመለካከትና አንድን  አጠቃላይ ነገር ወስዶ ከሱ በመነሳት ወደታች እየነጣጠሉ ምርምር ማድረግ ወደ ሀቀኛው መንገድ ያመራናል ብለው ያስተምራሉ። ለምሳሌ አንድ ህዝብ በአጠቃላይ ሲታይ ህዝብ ነው ከማለት በስተቀር ይህንም ያህል ሳይንሳዊ ትርጉም ሊሰጠን አይችልም። ከዚህ ወጣ በማለት ግን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለውን የህብረተሰብ ኃይል አሰላለፍና የሀብት ቁጥጥር ጉዳይና እንዲሁም የሀብት ክፍፍል በዝርዝር ስንመለከት የተሻለ ስዕል እንገኛለን። የበለጠ እየተነተን ስንሄድ ደግሞ ሀብት እንዴት እንደሚፈጠርና በየተኛውስ የህብረተሰብ ክፍል አብዛኛው ሀብት እንደሚመረትና በምንስ ዐይነት የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይከፋፈላል ብለን አንድ እርምጃ አልፍን ስንጠይቅና ስንመረምር አሁንም የተሻለ ስዕል እናገኛለን። ነገሩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ ለምሳሌ ወለድ(Interest)፣ ትርፍና(Profit) ኪራይ(Rent) በማርክሲዝም የፖሊቲካል ኢኮኖሚ መነሻቸው በቀጥታ በስራ-ክንውን ውስጥ የሚፈጠሩና በትርፍ የስራ ክንውን አማካይነት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚከፋፋሉ እንጂ፣ የኒዎ-ሊብራል ወይም ኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል ሁሉም እንደየአስተዋጽኦአቸው የሚደርሳቸው አይደለም። ይህም ማለት ሁለቱም የዕውነት መፈለጊያ መንገዶች ስለ አንድ ነገር ሲያወሩ የሚነሱበትና  ወደዚያ ለመድረስ የሚጓዙበት ስልት ይለያያል ማለት ነው። ውጤቱም እንደዚሁ።

       የመጨረሻዎችን ሁለቱን ሀቁን የመፈለጊያ መንገድ ትተን በመጀመሪያው በግሪኩ ስልጣኔ ላይ ስናተኩር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዕውነቱን ለመፈለግ የተደረገው ጥረት ወደ ተግባር ሲተረጎም የግሪክን ህዝብ ጭንቅላት እንዲከፈት ለማድረግ ይችላል። በመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላስፋዎች፣ በነ ታለስ የተቀደደው የተፈጥሮን ምንነት ለመረዳት የተደረገው የምርምር ዘዴ ለተከታታዩ ትውልድ ይበልጥ በምርምር እንዲገፉበት መንገዱን ይቀድለታል። በሶሎን አማካይነት የመጀመሪያው የፖለቲካ ሪፎርም ሲደረግ፣ የመጀመሪያዎች ተራማጅ ምሁሮች ሶፊስቶችም ጭምር ወደ ውጭ በመውጣት ክርክር ያደርጋሉ። የግብጽ ቄሶች ፍልስፍናን በቀሳውስቱ ብቻ የሚሽከረከርና የእግዚአብሄር ምስጢር አድርገው አፍነው የያዙትን ያህል፣ የግሪክ ፈላስፋዎች ግን ወደ ገበያ ላይ በማውጣት መወያያ በማድረግ ወጣቱ ራሱን እንዲጠይቅ ያደርጋሉ። በዚህም አማካይነት እነሶክረተስ፣ ፕላቶና ሌሎች የፍልስፍና፣ የሂሳብና የአርኪቴክቸር ሊቆች ብቅ ብቅ በማለት የግሪክን ህዝብ ኑሮ መለወጥ ይጀምራሉ። ከፍልስፍና ወደ ተግባር በመሸጋገር የሰው ልጅ በዕደ-ጥበብ፣ በቆንጆ አርክቴክተሮችና የከተማ ግንባታዎች እንዲሁም በሳይንስ አማካይነት ራሱን ለመለወጥ እንደሚችል ያረጋግጣሉ። የሰው ልጅ በዘልማድ ከኖረበት የአኗኗር ስልት ሲላቀቅና በአዲስ ሃሳብ መንፈሱን ሲያድስ በዕርግጥም የማሰብ ኃይሉ ስፋትንና ጥልቀትን እንደሚያገኝ በተግባር ያስመሰክራሉ። የግሪኩን ስልጣኔ አስመልክቶ እዚህ በርሊን ከተማ በተካሄደው ትልቅ ኤክዚቢሽን ላይ ፣ የግሪኩ ስልጣኔ በእርግጥስ ተግባራዊ የነበረ ነው ወይስ ዝም ብሎ ፍልስፍና ብቻ ነው የሚለውን ስመለከት የተገነዘብኩት፣ በዚያን ጊዜ የተሰሩት እጅግ የሚያማምሩ የዕደ-ጥበብ ስራዎችና ከዕብነ-በረድ የተሰሩ የቆሙ የተለያዩ የሰው ልጅ ቅርጾችን ነው። ከቤት አሰራር አንስቶ በወርቅና እንዲሁም ብርና ኬራሚክ የተሰሩ በዐይን የሚታዩና በእጅ የሚዳሰሱ ውብ ስራዎች የሚያረጋግጡት በእርግጥም የግሪኩ ስልጣኔ ወሬ ሳይሆን በፍልስፍና አማካይነት በተግባር የተተረጎመ መሆኑን ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ይህ ዕውነቱን ለመፈለግ የተደረገው ትግል በግሪክ ቄሶች አማካይነት ወደ ዛሬይቱ ኢስታንቡል፣ ድሮ ኮንስታንቲኖፕል ተብላ በምትጠራው በተግባር እየተመነዘረ የመጣውና ቀስ በቀስም የአውሮፓን ምድር ሊያዳርስ የቻለው። ይህ ብቻ አይደለም። ለምዕራብ አውሮፓም የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት የጣለው ይኸው የግሪኩ ፍልስፍና ነው። አውሮፓውያኖች ካለግሪኩ ፍልስፍናና የሳይንስ መሰረት የዛሬውን ምጥቀት በፍጹም ሊቀዳጁ አይቸሉም ነበር።

       አንድ ህብረተሰብ የቆመበትን ስርዓትና የህዝቡን የህሊና ሁኔታ በመተንተንና ከዚያ ተነሰቶ አንድን ህብረተሰብ ለመገንባት በሚደረገው ፍላጎትና ዕቅድ መሀከል ትልቅ ልዩነት አለ። የአንድ ህብረተሰብ ዕድል ወይም ዕድገት ይህንን ወይም ያንን ርዕይ እንከተላለን በሚሉ የህብረተሰብ ኃይሎች መሀከል በሚደረግ ትግል የሚወሰን ይሆናል። ይሁንና ግን ተጨባጩን ሁኔታ በማንበብና በመተንተን፣ ከዚያ ተነስቶ ህብረተሰብአዊ ዕቅድ በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ መሀከል ግጭቶችና ልዩነቶች ይኖራሉ። በሌላ ወገን ግን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለስልጣን ከሚታገሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ኃይሎች ባሻገር የራሳቸውን ርዕይ ተግባራዊ እንዲሆንላቸው የሚሹ የተለያዩ ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ። ምናልባት አንደኛው ኃይል ከጠቅላላው የህብረተሰብ ጥቅም አንጻር በመነሳት ራዕዩን ተግባራዊ እንዲሆንለት ሲታገል፣ ሌላው ደግሞ ከተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም  ብቻ በመነሳት በአገዛዙ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያልተቆጠበ ትግል ያደርጋል። እንደህብረተሰቡ የማቴሪያል ዕድገትና ንቃተ-ህሊና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመንግስት ፖሊሲ ላይ የግዴታ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ማለት ነው። የህበረተሰቡ ንቃተ-ህሊና ደካማ ከሆነና ጠበብ ያለ የምሁር ኃይል ካለ አንድ አገዛዝ እሱ በመሰለው መልክ „ህልሙን“ ተግባራዊ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት ከሃሳብ ይልቅ ጉልበት የበላይነትን በመቀዳጀት ህብረተሰቡን ወደ ማይሆን አቅጣጫ ይወስዳል። በታሪክ ውስጥ በተቻለ መጠን መንግስታትን ሰብአዊ ለማድረግና አንድ ህብረተሰቡን ስርዓት በአለው መልክ ለማስተዳደር ያሚያስችል ህብረተሰብአዊ ዕቅድ እንዲወጣና ተግባራዊ እንዲሆን ትግል ቢደረግም የመጨረሻ መጨረሻ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገትና አቅጣጫ የሚወስነው ኃይል ሀብትን የሚቆጣጠረው የህብረተሰብ ክፍል በመንግስቱ መኪናና የመንግስቱን መኪና በሚቆጣጠሩት ሰዎች ላይ በሚያደርገው ተጽዕኖ ነው። በሌላ አነጋገር ከአንድ የተወሰነ ወቅት በኋላ አንድ ህብረተሰብ የራሱን ውስጠ-ኃይል (Dynamism) በመያዝ፣ በተለይም ህብረተሰብአዊ ስምምነት እንዲኖር የሚፈልጉ የተሻለ የጥበብና የሳይንስ አመለካከት ያላቸው ምሁሮች እየተገፈተሩ፣ ስልጣንና ሀብትን የጨበጡ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ምሁሮች ደግሞ የራሳቸውን ቲዎሪና ሳይንስ የሚሉትን በማዳበርና ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ ህብረተሰቡ በአንድ ዶግማ እንዲመራ ያደርጋሉ። በአውሮፓ ምድር ውስጥ በተለይም በኤምፒሪሲዝም ላይ የተመሰረተው ህብረተሰብአዊ ሳይንስ በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ በሶክራተስና በፕላቶ እንዲሁም ደግሞ በሬናሳንስ ምሁሮች፣ ከዚያም በኋላ በጀርመን ክላሲኮች የፈለቁትና የዳበሩት ሳይንስና ፍልስፍናዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የድራማ ስራዎች ቦታ እንዳይኖራቸው በማደረግ ሀብትን በሚቆጣጠረውና በሌላው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል ግልጽ የሆነ የህብረተሰብ አሰላለፍ እንዲፈጠር ተደረገ። ከትምህርት ዕቅድ አንስቶ ማን ማን ከፍተኛ ትምህርት ቤት መግባት ይችላል እስከሚለው ድረስና፣ ከኢኮኖሚ ፖሊሲ አንስቶ ልዩ ልዩ የሀብት ክፍፍል መሳሪያዎች ድረስ የዳበሩት ዘዴዎች የሚያረጋግጡት ያለውን ህብረተሰብአዊ ልዩነትና የሀብት ክፍፍል የሚያረጋግጡና በርዕዮተ-ዓለም ሽፋን ተወጥረው ለአብዛኛው ህዝብ ግልጽ እንዳይሆኑ ተደርገው የተዋቀሩ ህብረተሰብን የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች ናቸው። ዛሬ በሊበራል ዲሞክራሲና በነፃ ገበያ ስም የሚካሄደው ማታለልና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ከህግ ፊት በእኩል ሊታዩ የሚችሉ ናቸው የሚለው ልፈፋና በወረቀት ላይ የሰፈረ ህግ ያለውን ተጨባጭ የሀብት ክፍፍልና የስልጣን አያያዝ ለመሸፈን የሚደረግ ማደንቆሪያ ቅስቀሳ ነው። በምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችና በታላቁ አሜሪካ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያረጋግጠው የየመንግስታቱን መኪናና ፖሊሲዎች ሎቢስቶች የሚቆጣጠሩትና የሚደነግጉት ነው። በሌላ አነጋገር፣ እነ ፕላቶ ያፈለቁት የኦሊጋርኪ አስተሳሰብ፣ በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ ማርክስ ያዳበረው የመደብ ትግልና ሀብትን በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥጥር ውስጥ የማድረጉ ጉዳይ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገትና ሂደት፣ እንዲሁም ደግሞ ሚዛናዊ በሆነ መልክ መጓዝ ወይም አለመጓዝ የጦርነትንም ጉዳይ ጨምሮ በአለው የኃይል አሰላለፍ የሚወሰን መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ስንነሳና በካፒታሊስት አገሮችም ውስጥ የሰፈነውን የሃሳብ መዘበራረቅም ሆነ መሸነፍ ስንመለከት ሊበራሎችና ኒዎ-ሊበራሎች እንደሚሉት ህብረተሰቦች በገበያው ህግ መሰረት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚተዳደሩ አይደሉም። ከፍተኛም ሆነ መለስተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ የሚወጡት አዳዲስ ቀውሱን ረገብ ማድረጊያ መሳሪያዎች ችግሩን የሚያስተላልፉና ውስብስብ የሚያደርጉ እንጂ ለቀውሱ ዋናው ምክንያት የሆነውን ለመዋጋት የሚያስችሉ  አይደሉም። ይሁንና በካፒታለስት አገሮች በኢንስቲቱሽኖችና በፓርቲዎች መሀከል አንድ ዐይነት አመለካከት ቢኖርም፣ በሌላ ወገን ግን አዳዲስ ቀውስ በተከሰተና ህብረተሰብአዊ ተቀባይነት የሌላቸው ፕሮጀክቶች መንግስታት ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥሩ ይህንን የሚቃወሙ ህዝባዊ ድርጅቶች በመቋቋም ፕሮጀክቶችን ለማጨናገፍ ይሞክራሉ። የየራሳቸውን አማራጭ መፍትሄ በማቅረብ በተሻለ መንገድ እንዲፈታና ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ያመለክታሉ። እንደ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ዕምነትና የዕውቀት ጥልቀት ለዘብ ያሉ ወይም “ከረር“ ያሉ መፍትሄዎች በማቅረብ በመንግስት ተቀባይነት ባላቸው ፓርቲዎች ላይ ግፊት ያደርጋሉ። በየወቅቱ በካፒታሊስት አገሮች በፓርቲዎች መሀከል የሚደረገው መከፋፈልና የሃሳብ ልዩነት፣ ወይም በጥምር በሚገዙ መሀከል ከተወሰነ በኋላ የአገዛዙ መበታተን የሚያመለክተው የየአገሮችን የቅራኔዎች ውስብስብነት ብቻ ሳይሆን፣ ፓርቲዎች ከጠቅላላው ህብረተስብአዊ ውስጠ-ኃይል ጋር ለመጓዝ እንደማይችሉና ኢኮኖሚያዊ ቀውስም ሲከሰት በሎቢስቶች ግፊት ስራቸውን በገለልተኝነት ለመስራት የማይችሉ መሆናቸውን ነው።

       ወደ መከረኛዋ ኢትዮጵያችን ስንመጣ ዛሬ በተከታታይ የሚጻፉት አገዛዙንም ሆነ የምዕራቡን ዓለም ዕርዳታና የሙጥኝ ማለት የሚያመለከቱ ጽሁፎች ከነዚህ ሶስቱ መንገዶች የትኛውን እንደሚከተሉ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ላይ እንዳልኩት በጋዜጠኛ አቀራረብና አንድን ህብረተሰብ ለመለወጥ በሚታገሉ ጸሀፊዎች መሀከል የሰማይና የምድርን ያህል ልዩነት አለ። አንድን ህብረተሰብ ለመለወጥ የሚታገሉና የሚጽፉ ኃይሎች በምንም ዐይነት ከሶስቱ መንገዶች ውጭ ወጥተው ስለአገራቸው የማቴሪያልና የአተሳሰብ ሁኔታ ትንተና ለሲጡ አይችሉም። በሌላ ወገን ግን በዓለም ላይ የተስፋፋው ዝብርቅርቅ ሁኔታና የግሎባል ኢኮኖሚ ከቁጥጥር ውስጥ መውጣት በተለይም ባለፈው ሃያ ዐመት ዓለምን በአንድ ርዕዮተ-ዓለም ሽፋን ስር ለማምጣት የተደረገውንና የሚደረገውን ትግል በቅጡ ለማየት እንዳንችል ጋርዶናል። ይሁንና ደግሞ የሶሻሊስቱ ካምፕ መፈራረሱ የራሱንም አዎንታዊ ጎን ይዞ ብቅ ሊል ችሏል። የሰው ልጅ ሙሉ ነጻነቱን ሊቀዳጅ የሚችለውና ተፈጥሮን ሊረካባትና ሊንከባከባት የሚችለው በዚህ በተኮላሸ ስርዓት ሳይሆን፣ የግሪክ ክላሲኮችም ሆነ የህንድና የቻይና ፈላስፋዎች ያስተማሩት የመንፈስን የበላይነት የሚያረጋግጠው ጥበብ በግለሰቦች ጭንቅላት ውስጥ ሲገባና የሰው ልጅ ከማቴሪያል ደስታ ይልቅ መንፈሳዊ ደስታን ቢቀዳጅ ለራሱ ጤንነት ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የዓለም ህዝብም ሰላም መስፈን መረጋገጥ ይሆናል የሚለው ተቀባይነትን ሲያገኝ ብቻ ነው። ስለዚህም የሶሻሊስቱ ካምፕ የፈራረሰውን ያህል ካፒታሊዝምና ሊበራል ዲሞክራሲ ሃያ ዓመት ያህል ከተንደፋደፉ በኋላና የዓለም ህዝብ የመጨረሻውን ደስታ በሊበራል ዲሞክራሲ ብቻ ነው ሊጎናጸፍ የሚችለው፤ ከዚህ በላይ ዘልቆ ሊሄድ አይችልም የሚለውን በሄገል ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ በፉኩማያ የተሰበከውን የርዕዮተ-ዓለም ጣሪያ በፊናንስና በኢኮኖሚ ቀውስ እየታየና አዳዲስ ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎች እየፈጠረ እንደሆነ በግልጽ የምናየው ነው። በቅርቡ ከማርክሲዝም አስተሳሰብ ውጭ ተላቀው ብቅ ብቅ ያሉት ግሩም የኢኮኖሚም ሆኑ የፍልስፍና መጽሀፎች የሚያረጋግጡት ክፍቱ ህብረተሰብ(The Open Society) በሊበራል ዲሞክራሲና በእንደዚህ ዐይነቱ ልቅ የግሎባል ካፒታሊዝም የበላይነት ሊገለጽና በየአገሮች የሚታዩትም ህብረተሰብአዊና የአካባቢ ቀውሶች መፍትሄ ሊያገኙ እንደማይችሉ ነው። በሌላ አነጋገር ትግሉ ከሊበራል ዲሞክራሲና ከግሎባል ካፒታሊዝም ባሻገር መታያት ያለበት ነው ማለት ነው። የዓለም ህብረተሰብ አንገብጋቢ ጥያቄ ከተራ የኢኮኖሚ ዕድገት አልፎ በስልጣኔ ብቻ ሊፈታ እንደሚችል ነው ሁኔታው የሚያሳስበን።

       ከዚህ ስንነሳና ወደ ተጨባጩ አገራችን ሁኔታና ከምዕራቡ ዓለም ጋር መተሳሰርና መደጋገፍ እንዲሁም በአገራችን ምድር ስልጣኔ እንዳይታይና ህዝባችንም በዘለዓለማዊ ውዝግብ እንዲኖር የሚደረገው የተሰመጣጠረና በተንኮለኞች የተሸረበና ብዙዎቻችን ሳናውቅ የዚህ አሻጥር ሰለባ በመሆን በህዝባችን ላይ ዘመቻ የምናካሂድ የፖለቲካውን ቅንብር ለመረዳት በቀጥታ ከምናየው አልፈን በመሄድ ምርምር ማድረግ እንዳለብን ነው። ስለዚህም ዛሬ በአገራችን ላይ የሰፈነውን አገዛዝና የተመሰቃቀለ ድርጊት በአንድ በኩል ከተጨባጩ የማቴሪያልና የባህል ሁኔታ አንጻር መመርመር ሲገባን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰለጠንኩ የሚለው የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካና የፊናንስ ኦሊጋርኪዎች የሶፊስቶችን የውሸት ቅስቀሳ የአገዛዝ ስልት በመጠቀም እንዴት አድርጎ ደካማ አስተሳሰብ ባላቸው አገዛዞች ጭንቅላትና የስልጣን አውታር ውስጥ በመግባት አንድ ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንዳይችልና ዕውነተኛ ስልጣኔን እንዳይጎናጸፍ የሚሸርበው ተንኮልና ግልጽ ወረራ ተነጣጥለው መታየት እንደማይችሉ ነው። ይህን መተሳሰርና መላላስ በረድፍ በረድፉ እንመልከት። በመጀመሪያ የኢትዮጵያን ስርዓት አወቃቀር አጠር ባለ መልክ ለማየት እንሞክር።

የወያኔን ባህርይና የተፈጠረበትን ህብረተሰብ የመረዳት ችግር!

       ባላፉት 19ኝ ዐመታት የወያኔን አገዛዝ ምንነት ለመግለጽ የምንጠቀምባቸው ጽንሰ-ሃሳቦች አምባገነን፣ የአልባኒያው ዐይነት ስታሊኒስታዊ አገዛዝ ወይም ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚያራምድ… ወዘተ. እያልን ለማሳመን በመሞከር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱን በሺህ ተንኮሎች የተካነን አገዛዝ እራሱ አምንበታለሁ ብሎ ከተቀበለው ርዕዮተ-ዓለም ጋር አስተሳስሮ ባህርዩን ለመተንተን በጣም እንደሚያሰቸግር ይገባኛል። ሌሎችን ለማሳመን ራሱ አገዛዙም ሆነ አንድ ሰው እንደዚህ ነኝ፣ እንደዚህ ብላችሁ ጥሩኝ ብሎ ሲናገር እሱን አምኖ ከመቀበልና ትንተና ከመስጠት የቀለለ ነገር የለም። ለመወንጀልም ሆነ ለማስጠላትም አጭሩ መንገድ ይኸኛው ስለሆነ ብዙዎቻችን ሳንጨነቅ፣ ሳናወጣና ሳናወርድ እሱ እንደዚህ ነኝ ብሎ በተናገረው ሃሳብ ላይ እንረባረባለን። በዚህም ዕውነተኛውን የትግል ፈለግ ያገኘን መስሎን ብዙ ሰዎችን ለማሳመን እንሞክራለን። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በአንድ አስተሳሰብ መታነጽ አብሮን የተፈጠረ አይደለም። ከባህልና ከአካባቢ ወይም በትምህርት ዓለም ውስጥ ከቀሰምነውና ተቀባይነት ያገኘውን አንድን ህብረተሰብ የመቃኛ ዘዴ ከራሳችን ጋራ በማዋሃድ ነው። ሶክራተስ እንደሚለው አእምሮ ወይም መንፈስ ልክ እንደሰውነት በጭንቅላት ጂምናስቲክ  ሊታነፅ የሚችል ነው። በተለያዩ ሁኔታዎች የሰው ልጅ አስተሳሰብ ጥሩና ቆንጆ፣ አታላይና ነገሮችን ደፋፍኖ የሚያልፍ ወይም ሀቁን የሚፈልግ፣ ተንኮለኛና የሰውን ስም በሆነው ባልሆነው የሚያጠፋ ወይም የማያጠፋና ዝምተኛ፣ ተቆጭኝና አመጸኛ ወይም ትዕግስተኛ፣ አርቆ የሚያስብና ወይም በጠባቡ የሚያስብ፣ አክራሪ የሆነና ያልሆነ፣ ለሰው ልጅ ርህሩህ የሆነና ያልሆነ፣ ከማቴሪሊያዊ የኑሮ ሁኔታ ይልቅ የመንፈስን ደስታ የሚያስቀድም፣ ለስልጣኔ የቆመ ወይም ደግሞ ለገበያ ኢኮኖሚ ሽንጡን ገትሮ የሚታገል… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ባህሪዎች በተወሰነ የህብርተሰብ ውስጥና በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚነዛ ርዕዮተ-ዓለም እንደየሁኔታው በሰው ጭንቅላት ውስጥ ገብተው የአንድን ሰው አስተሳሰብ ወጥረው የሚይዙና በዚያው ድርቅ እንዲልና  ድርጊቱንም የሚወስኑ ናቸው። ፕላቶ እንደሚለው ማንኛውም ሰው ከሃሳብ ጋር ቢፈጠርም ተፈጥሮአዊ አስተሳሰቡ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ እንደኖርም በተወሰዱና በተስፋፉ አነጋገሮችና የአኗኗር ስልቶች ሊቀረጽ ይችላል። በዚህ በየጊዜው በሚለዋወጥና በብልጭልጭ ዓለም ደግሞ የአንድ ሰው ጭንቅላት ያልረጋና ያለበሰለ ከሆነ ዝም ብሎ የሚወረወሩ አስተሳሰቦችን ተቀብሎ እሱን ማሰተጋባት እንደፈሊጥ ይያዛል። ይሁንና ግን በፍሮይድ ዕምነት የማንኛውም  ሰው አስተሳሰብ ከተወለደ ጀምሮ እስከ አምስት ዐመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው የሚወሰነው። በሌላ አነጋር አርቆ የማሰብ ያለማሰብ፣ ጥያቄ የመጠየቅ ያለመጠየቅ፣ ተንኮለኛ የመሆን ያለመሆን …ወዘተ. እስከ አምስት ዐመት ባለ ዕድሜ ውስጥ ነው በሰው ጭንቅላት ውስጥ ተቀርጸው የሚቀሩት። አንድ ሰው የርዕዮተ-ዓለም ተገዢ መሆንና አለመሆን፣ በዚያው ጸንቶ መታገልና አለመታገል እስከ አምስት ዐመት ባለው በህርይ ውስጥ በሚደረገው የጭንቅላት ግንባታ ነው የሚወሰነው። ይህ ቢሆን ኑሮ የእስላምን ሃይማኖት ተከታይ በሙሉ አክራሪ በሆነ ነበር። ሁላችንም ከቤተሰብአችን ወይም ከአካባቢያችን ባገኘነው ዕምነትና ርዕዮተ-ዓለም ብቻ ጸንተን በመቆየት እሱን ለማራመድ በታገልን ነበር። ይሁንና ግን እንደፍላጎታችንና በጥቂት ነገር እማንረካ ከሆነ በየጊዜው አዳዲስ ርዕዮተ-ዓለምም ሆነ የመንፈስ ማጽንኛ መንገድ ለመፈለግ ጥረት እናደርጋለን። ሁሉ ነገር ግራ የሚያጋባ ከሆነና በመንፈስ ጭንቀት   የምንሰቃይ ከሆነ ደግሞ አንዳንዶቻችን ሃይማኖተኛ በመሆን ዕውነተኛውን መንገድ ያገኘን ይመስለናል።

       ለምን እንደሆን አይገባኝም ብዙ ጊዜ መጽሀፎችም ሆነ አርቲክሎች ስንጽፍ ከኢትዮጵያ ነባራዊና የመንፈስ ሁኔታ ጋር ለማገናኘት በፍጹም አንችልም። ከግሪኩ የጥንት ታሪክ ጀምሮ እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስና በነሺለርና ጎቴ ዘመን ሁሉም ጸሀፊዎችና የድራማ ሰዎች ይተነትኑ የነበረው ከአገራቸው ሁኔታ በመነሳት ነው። ይሁንና ግን እነ ዳንቴም ሆነ ሼክስፔር እንዲሁም ሺለር 㜎ይጠቀምቡት የነበረው የምርምርና የአጻጻፍ ስልት የእነ ፕላቶንን የምርምር ዘዴና በግሪኩ ዘመን በቲያትር መልክ ይቀርብ የነበረውን የትራጂክ ቲያትር በጊዜው ከነበረው የአገራቸው ሁኔታ ጋር በማቀናጀት ነበር። ለዕድገትና ለስልጣኔ እንቅፋት የነበሩ የአስተሳሰብ ወልጋዳነትና እልክነት በቲያትር መልክ በማሳየት አገዛዞች ከእንደዚህ ዐይነት ባህሪያቸው ተላቀው ለስልጣኔ እንዲቆሙ በማሳሰብ ነበር። የሼክስፔርም ሆነ የሺለር ስራዎች በተለይም የገዢዎችን ተለዋዋጭ ባህርይና ቆራጥ አለመሆንና የባህርይ ፈሳሽነት በማሳየት ነበር ለማሳየትና ለማስተማር ይታገሉ የነበረው። ስራቸውም ሙሉ በሙሉ ሰብአዊነት የተሞላውና የሃሳብን የበላይነት ወይም በሁኔታዎች ሊሸነፍ የሚችል መሆኑን የሚያመለክት ነበር። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ አስተሳሰብ ቀና ሆኖ እስካልታነጸ ድረስና አመለካከቱ ጠባብ ከሆነ የማጥፋት ኃይሉ ከፍ እንደሚል በመታወቁ ይህንን ተለዋዋጭ ባህርይ በድራማም ሆነ በስነ-ጽሁፍ መልክ በመግለጽና በመተንተን የህብረተሰቦችን ዕድገት መልክ ለማሲያዝ ትግል ይደረግ ነበር። ኤንላይትሜንት የሚባለው ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴም የሚያስተምረን አንድ ህብረተሰብ ከልማዳዊ አሰራር በመላቀቅና ወደ ሳይንስ በማምራት በተፈጥሮ ላይ ያለውን የበላይነት በማረጋገጥ ነጻነትን እንዲቀዳጅ ነው። ጽንሰ-ሃሳቡ የሚያሰተምረን በጊዜው የሰፈነውን የአሪስቶክራሲና የባላባት መደብ ወግ-አጥባቂነት ስርዓት በመቃወም ግለሰብአዊ ነጻነትን በማስቀደም የሰውን ልጅ ፈጠራ ለማረጋገጥ ነበር።  ባጭሩ ከአስራ አምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተካሄደው ትግል የአውሮፓውን የአገዛዝ ስርዓት ኋላ-ቀር ከሆነ የአኗኗር ፍልስፍና አላቆ ፈጠራን በማሰቀደም ብርሃንን ለማፈናጠቅ ነው።

       ወደ አገራችን ስንመጣ ያለው ችግር ይህንን ከኋላ-ቀርነት ለመላቀቅ የተደረገውን አስቸጋሪ ጉዞና የአገራችንን ውስጣዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ለመረዳት ያለመፈለግ ወይም ያለመቻል ነው። በህዝባችን ጭንቅላትና የአኗኗር ስልት ላይ ፊዩዳሊዝምና የክርስትና ሃይማኖት ዕምነት ተጽዕኖ አልነበራቸውም ወይ?  የኢትዮጵያ ተገልሎ መኖር  በውስጥ የነበረውን የአመራረት ስልትና የምርት ኃይሎች ዕድገት ውስን ሆኖ እንዲቀር አላደረገውም ወይ? የዕደ-ጥበብ ስራ አለማደግ፣ የንግድ እንቅስቃሴ አለመኖርና የከተማ ዕድገት አለመታየት የሰው አስተሳሰብ ጠባብ ሆኖ እንዲታነጽ 㗹አላደረገውም ወይ? ባጭሩ ጥንታዊው የአኗኗር ስልት ለብዙ መቶ ዐመታት ተንሰራፍቶ በመኖሩ እስከዛሬ ድረስ ያለውን አስተሳሰባችንን ሙጥኝ አድርጎ አልያዘውም ወይ? በሃያኛው ክፈለ-ዘመን „ዘመናዊነት“ የሚባለው የዕድገት ፈለግ ሲገባ የህብረተሰብአችንን አወቃቀር መልክ አሲያዘው ወይስ አዘበራረቀው? አገባቡስ በዕውቅ ላይ የተመሰረተ ነው ወይ? ወይስ በጊዜው የነበረው የኃይል አሰላለፍ የዕድገቱን ፈለግ ውስን በማድረግ የህብረተሰብአችንን አቅጣጫ ሊያዘበራረቀው አልቻለም ወይ?  እ.አ.አ ከ1942 ዓ.ም በኋላ የተከሰተው አዲስ ሁኔታና የኢንዱስትሪ ተከላ በህብረተሰብአችን ውስጥ ልዩ ዐይነት ክስተትን አልፈጠሩም ወይ? የአነጋገር ስልት አለዋወጥ፣ አረማመድና አለባበስ እንዲሁም ደግሞ ዘመናዊ ነኝ በሚለው አዲስ በተፈጠረው የህብረተሰብ ክፍልና በሰፊው ህዝብ መሀከል የነበረው ግኑኝነትና መራራቅ በአዲሱ „የዘመናዊነት ፈለግ“ ሊወሰኑ አልቻሉም ወይ? ከአስተሳሰብ ለውጥ በፊት ቀድሞ የገባው የተመጠነ የኢንዱስትሪ ተከላና የተበላሸ የከተማ አሰራርና አመሰራረት አስተሳሰባችንን አለዘበራረቁትም ወይ? ዘመናዊነትና ኋላ-ቀርነት ወይንም የፊዩዳል ኢኮኖሚ እዚያው በዚያው ጭንቅላታችን ውስጥ በመላወስ አስተሳሰባችንና ሂደታችንና አለወሰኑም ወይ?  ባጭሩ በ50ዎቹ ብቅ ያለው ዘመናዊ የሚባለው ወይም አዲሱ ትውልድ በአስተሳሰቡ የጠራ ሆነ ወይስ ራሱ ተምታቶበት ለተከታዩም ትውልድ ሁኔታዎችን አበላሽቶ አለፈ ወይ? ብዙ መነሳትና መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦች አንስቶ ውይይት ሳይደረግ የዛሬውን አገዛዝ በጥቂት ጽንሰ-ሃሳቦች ብቻ ለመግለጽ መሞከር ካለን መሰረታዊ ችግር በፍጹም ሊያላቅቅን አይችልም። ማንኛውም አገዛዝ ከዚያው ህብረተሰብ ውስጥ የፈለቀ በመሆኑ ድርጊቱ በሙሉ ለዘመናት በተላለፉ የአስራር ኖርሞችና ባህርይዎች ይወሰናሉ። ፈረንጆች እንደሚሉት ማንኛውም ህብረተሰብ የሚያገኘው አገዛዝ ራሱ የፈጠረውን ወይም ደግሞ ማግኘት ያለበትን ነው።Every Society gets what it deserves!  ከዚህ ውጭ በፍጹም ሊሆን አይችልም። ይህ አቀራረብ ግን ከዚህ ቀደም የነበሩትን ገዢዎችንም ሆነ የዛሬውን አገዛዝ ከወንጀል ነጻ ሊያደርጋቸው የሚችል አይደለም። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ግን የሚነሳው ጥያቄ ስልጣን የጨበጡት ገዢዎች ሰው እንደመሆናቸው መጠን የሚያደርጉትን ድርጊት በየጊዜው የመመርመርና ራስን የመጠየቅ፣ ስህተት ከተሰራ ደግሞ ለማረም የማያስችላቸው ጉዳይ ምንድ ነው? ጥፋት የሚያጠፉ ከሆነ ለምንድነው አምረረው በዚያው የሚገፉበት?  የሚገፋፋቸውስ ነገር ምንድ ነው? ሀብትና ስልጣን እስከዚህ ድረስ የሰውን ጭንቅላት ዕውር ያደርጋሉ ወይም ያደነዝዛሉ ወይ? እነዚህን ነው ከአገራችን የረዢም ጊዜ የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክና የባህል ሁኔታ አንፃር እያነሳን መወያየት ያለብን። ይህንን ማድረግ የማይችል ወይም የማይፈልግ የምሁር ትውልድ በምንም ዐይነት ለስልጣኔ አስተዋጽኦ ሊያበረክት አይችልም። በሊበራሊዝምና በነጻ ገበያ እንዲሁም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ውስን አመለካከቶች ዙሪያ የሚደረገው መራወጥ የትም አያደርሰንም። ሁኔታውን ከማጨለም በስተቀር።

       ለመሆኑ አንድ ጤናማ ጭንቅላት ያለው ምሁር በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ቢያንስ ከአስራሶስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለስምንት መቶ ዐመት ያህል የፊዩዳሉ ስርዓት አልነገሰም ብሎ የሚያምን አለ ወይ? የሚያምን ከሌለ እንደዚህ ዐይነቱ ምሁር ጭንቅላቱ የተጋረደ ወይም ደግሞ „በራሱ ቲዎሪ“ ብቻ እየተመራ የታሪክንና የህብረተሰብ ክንውንን ለመቀበል የማይፈልግ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን ሁላችንም አምነን የምንቀበል ከሆነ ፊዩዳሊዝምን እንደቁንጽል አስተሳሰብ መገንዘብ የለብንም። ዝም ተብሎ መሬት ባላቸውና በሌላቸው፣ ወይም በጨቋኝና በተጨቋኝ አስተሳሰቦች ብቻ ሊገለጽ የሚችል አይደለም። በታሪክ አጋጣሚም ሆነ የኋላ ኋላ በዕውቅ ከተዋቀረ በኋላ፣ ፊዩዳሊዝም የህብረተሰብአችንን አጠቃላይ የአኗኗር ስልት፣ የሰው ከሰው ግኑኝነት፣ የባህል ሁኔታ፣ አጠቃላይ የርዕዮተ-ዓለም ጉዳይ፣ ህብረተሰብአችን በአጠቃላይ ሲታይ ከተፈጥሮ ጋር ያለውንና የሚኖረውን ግኑኝነት፣ የአመራረት ስልትና የፈጠራ ጉዳይ፣ የምርት-ኃይሎች ዕድገት ጉዳይ፣ ወይም በዚያው እንዳለ አንቆ መያዝ፣ የገበያ ዕድገት ጉዳይና ከዚህ ጋር ተያይዞ በገንዘብ ዕድገት አማካይነትና በገበያ ዕድገት ምክንያት ሊፈጠር የሚችል የከተማ ዕድገት ወይም የዚህ ሁኔታ ባለበት ቀጭጮ የመቅረት ጉዳይ፣ የቤት አሰራር ጉዳይና በየጊዜው እየተሻሻለ የመሄድ ጉዳይና ወይም ያለመሻሻል፣ የሙዚቃ ጉዳይና በአጠቃላይ ሲታይ ተፈጥሮንና የአኗኗር ስልትን በሙዚቃ የመቃኘት ጉዳይ፣ አንዱ ለሌላው ሰው የሚኖረው ፍቅርና የሰብአዊነት ጉዳይ …ወዘተ. በሌላ ሳይሆን በነበረው ስርዓት የሚደነገጉና በሱም አማካይነት ሊገለጹ የሚችሉ ናቸው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው ? ወደድንም ጠላንም የህበረተሰብአችን ዕድገት፣ በሰፊውና በጥልቀት የማሰቡ ጉዳይ በጊዜው በነበረው ስርዓት ሊወሰን ችሏል ማለት ነው። በብዙ ህብረተሰቦች እንደተረጋገጠው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ እንደልማድና እንደባህል የተወሰዱ የአኗኗርና የአሰራር ስልቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር በተለይም በየጊዜው ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎችን ጭንቅላት ጨምድደው በመያዝ አንድ አገዛዝ ለዕድገትና ለአጠቃላይ የባህል ዕምርታ እንቅፋት እንደሚሆን በታሪክ የተረጋገጠ ነው። ህዝብም የኋላ-ቀር አሰራርና የልማዳዊ ባህል ሰለባ በመሆን እዚያው በዚያው እንደሚንደፋደፍና አዲስ ነገር ለመፍጠርና ኑሮውን ለማሻሻል ዝግጁ እንደማይሆን ነው። ይህ ባይሆን ኑሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ዕድገት ወይም ድህነት ሁሉንም የዓለም ማህበረሰብ ባዳረሰ ወይም እንቅ አድርጎ በያዘ ነበር።

       እንደገና ወደ ተጨባጩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ስንመጣ የፊዩዳሊዝም ጽንስ የተጣለው ዛሬ ትግሬ ተብሎ በሚጠራው ክልል ውስጥ ነው። የክርስትና ሃይማኖትም ተቀባይነት ያገኘውና ሌሎች አምልክዖችን እየተጋፋ የመጣውና በጉልበት በአገዛዙ አማካይነት ህዝቡ እንዲቀበለው የተደረገው በዚሁ የግዛት ክልል ውስጥ ነው። የፊዩዳሊዝም ጽንስ መጣል፣ የክርስትና ሃይማኖት ተቀባይነት ማግኘትና መሰበክ፣ እንዲሁም ደግሞ ሰፊው ህዝብ ለአገዛዙና ለቤተክርስቲያን ገባሪ መሆን፣ የሰው አስተሳሰብ ውስን እንዲሆንና የመኖር ትርጉም በዚህ ዐይነቱ አመለካከት ዙሪያ እንዲሽከረከር ሊያደርገው በቃ። በእኔ ዕምነት በተለይም የክርስትና ዕምነት ቶሎ ተቀባይነት ማግኘት የህዝቡን አስተሳሰብ ውስን በማድረግ በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ እንዲያደርግ አስችሎታል። አርቆ አሳቢነት(Rationalism or Logos) ቦታ እንዳይኖረውና እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዳይወሰንና የተፈጥሮ ሰለባ እንዲሆን አስገድዶታል። ለምሳሌ ከጥንታዊ አምልኮነት በቀጥታ ወደ ፍልስፍና የተላለፉት እንደግሪክ የመሳሰሉ፣ ወይም የቻይናና የህንድን የመንፈስ እንስቃሴን ስንመለከት ከሚቶሎጂ ወደ መንፈሳዊ ወይም ፍልስፍናዊ እንቅስቃሴ መሸጋገር ለእነዚህ አገሮች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያገኙና የተሻለ የዕድገት ፈለግን እንዲከተሉ አስችሏቸዋል ብል ምናልባት ስህተት አይሆንም። በአውሮፓ ውስጥም የምንመለከተው ይህንን ነው። የካቶሊክ ዕምነት በግሪኩ አርቆ-የማሰብ ፍልስፍና እንዲሸነፍ እስከተደረገ ድረስ አብዛኛው ህዝብ በጨለማ ዐለም ውስጥ እንዲኖር አስገድዶት ነበር። እንደዚህ ዐይነቱ በጨለማ የመኖር ሁኔታና የግዴታ በጭንቅላት ውስጥ ብርሃን ተፈናጥቆ የስልጣኔን ፈለግ መቅደድ በዳንቴ የአምላኮች ኮሜዲ አማካይነት የተገለጸና ህዝቦችና መንግስታት ከጨለማ አስተሳሰብ ተላቀው ብርሃንን አይተው ራሳቸውንና ተፈጥሮን ለውጠው ገነትን እንዲመሰረቱ የተቀደደበትን ሁኔታ መመልከት ይቻላል። ወደኛ አገር ስንመጣ ከሃይማኖት ዕምነት መስፋፋትና ስር መስደድ ጋር ተደምሮ በአብዛኛው በግብርና ላይ ብቻ የተወሰነውና የተመሰረተው „የሀብት ፈጠራ ዘዴ“ ለሌሎች የሀብት ማዳበሪያ የስራ ክፍፍል ዘዴዎች መንገዱን ክፍት ሊያደርግ አልቻልም። በጊዜው የነበረው የሩቅ ንግድ ግኑኝነት የአመራረት ስልቱንና ባህሉን ሊቀይረው በፍጹም አላስቻለውም። የሩቅ ንግድ ትርፍ ለአገዛዙ መጠቀሚያ ብቻ በመዋሉ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገቡ ነጋዴዎች እዚያው በመኖርና የስራ ክፍፍል በማዳበር ለዕድገት አስተዋጽኦ ሊያበርክቱ ሁኔታው አልፈቀደላቸውም። ሃይማኖትና ስርዓቱ አንድ ላይ እየተደጋገፉ ሲመጡና የህብረተሰቡን የአሰራር ስልት ሲወስኑ፣ ህዝቡ እንደህብረተሰብ እንዳይመሰረትና ከነበረበት ሁኔታ አልፎ የተሻለ የአመራረት ሰልትንና የአኗኗር ባህልን ማሳደግና ማዳበር እንዳይችል አንቀው ያዙት። ይህ ተደጋጋሚ የአሰራር ስልትና አሰልቺ ኑሮ መሰረት በመያዝ አገዛዙና ሃይማኖት ከዚህ በላይ የሰው ልጅ ተሻግሮ ለማለፍ የማይችል፣ በራሱ የማሰብ ኃይል ተፈጥሮን የሚለውጥ መሆኑ ቀርቶ የተፈጥሮ ተገዢ በመሆን ለረሃብና ለበሽታ እንዲሁም ለድንቁርና ሰለባ እንዲሚሆን ሳያውቁ ሁኔታውን አመቻቹ።

       ያም ሆነ ይህ የፊዩዳሊዝም ተጽእኖ በሰሜኑ የኢትዮጵያ የግዛት ክልል እጅግ አጥፊና እስከዛሬም ድረስ ስር ሰዶ አልላቀቀን ያለ ሰርዓት ነው። የሰው ተሰበጣጥሮ መኖርና ተጠራጣሪ መሆን፣ አጥብቆ አምላኪነት፣ በተፈጥሮ ላይ ያደረገው ዘመቻና የመሬቱ ድርቀት፣ በዚህ የኑሮው ሁኔታ መርካትና ይህንን እንደጉራ አድርጎ መውሰድ፣ የማያስፈልግ ኩራትና ስራን የመናቅ ጉዳይ፣ ዕልክነትና ሁሉንም ነገር በጉልበት ለመፍታት መሞከር፣ ሁሉም ባይሆን የተወሰነው ከሌላው የተለየ መሆኑን ለማሳየት መሞከር… ወዘተ. በአንድ በኩል የፊዩዳሊዝም ኖርም ስር ሰዶ የገባ መሆኑን ሲያመለክት፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ የምሁር እንቅስቃሴ ብቅ ለማለት ያለመቻል የህብረተሰበአችን ዕድገት ህግ ሆኖ አስተሳሰባችንና ድርጊታችንን ሊወስን ችሏል። የክርስትና ሃይማኖት ውስን የስልጣኔ ሚና ቢኖረውም በአጠቃላይ ሲታይ ሌሎች ዕምነቶች እንዳይዳብሩ የሰውን ጭንቅላት አፍኖ በመያዙ ሰፊው ህዝብ የረቀቀ አስተሳሰብ እንዳያዳብርና የኑሮውን ሁኔታ እንዳያሻሽል እድርጎታል። በዚህ ዐይነት የረዢም ጊዜ እዚያው በእዚያው የመንደፋደፍ የህብረተሰብ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ስርዓቱን ለማሻሻል ለውጦች ለማደረግ ትግል ቢደረግም በነበረው የኃይል አሰላለፍ ሊከሽፍ ችሏል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሃይማኖት የቴክኖሎጂ ዕድገት እንዳይመጣ በቀጥታ ይቃወም ነበር። በአፄ ምኒልክ ዘመን የእሳቸው አማካሪ የነበረው የሰዊዘርላንድ ዜጋ ኢንጂነር ከዝቅተኛው ቦታ ወደ ቤተመንግስታቸው እንጦጦ ተራራ ላይ ውሃ ማስገባት እንደሚቻል ይነግራቸዋል። እሳቸውም ሃሳቡን በመደገፍ ተግባራዊ እንዲያደርግ ይፈቅዱለታል። ካህናቱ ይህ የሰይጣን ስራ ነው ብለው አጥብቀው ይቃወሙታል። አፄ ምኒልክ እስቲ ሰርቶ ያሳየን ብለው ይነግሯቸዋል። ኢንጂነሩም ስራውን ጀምሮ ካጠናቀቀ በኋላ ውሃው ወደ ላይ እንዲወጣ ቧንቧውን ቢከፍት ውሃው መውጣት ይሳነዋል። ግራ ይገባዋል። ሲፈትሽ ዲንጋይ ተቀርቅሮበት ያገኛል። የቀሳውስቱም ተንኮል መሆኑን ይገነዘባል። በኋላ ውሃው ወደቤተመንግስት ወስጥ ገብቶ በማረጋገጥ የንጉሱን ድጋፍ ያገኛል። በአጭሩ፣ ከቦታ ቦታ ያለውን ልዩነት ወደ ጎን ትተን የፊዩዳሊዝምና የክርስትና ሃይማኖት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት የጠቅላላውን ህዝብ አስተሳሰብ ውስን በማድረግ ፈጣሪ እንዳይሆን አንቀው ይዘውታል። ለዕድገትም ጠንቅ በመሆን  በመንግስቱ መኪና ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ችለዋል። በዚህም በዚያም ብሎ ደግሞ ወደ ላይ የወጣውን የህብረተሰብ ክፍልና ተማርኩ የሚለውን ጉረኛና ኩሩ በማድረግ አስተሳሰቡ በፍጆታ አጠቃቀም ላይ ብቻ እንዲወሰን በማድረግ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የተለየ መሆኑን ማረጋገጫ ሆኖሎታል።

       በተለይም ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ድል ከተመታና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የካፒታሊስት ሎጂክና ገበያ ውስጥ ስትገባ እየተንጠባጠበ የገባው ዘመናዊነት የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ይበልጥ በንግድና በፍጆታ አጠቃቀም ላይ እንዲሰማራ በማድረግ የገበያ እንቅስቃሴ መሰረታዊ ለውጥ እንዳያመጣ አደረገ። አዲሱ በአዲስ አበባ ብቻ የተገነባው ዘመናዊ ቢሮክራሲ በአንድ በኩል አገዛዙን ከህብረተሰቡ ሲነጥለው፣ በሌላ ወገን በክፍለ-ሀገሮች የተዘረጋው ግማሽ ፊዩዳላዊና ሙሉ በሙሉ ከመሬት ጋር የተያያዘ የፊዩዳል ቢሮክራሲ ዕድገትንና ስልጣኔን የሚቀናቀኑ ሆኑ። ከክፍለ-ሀገራት አስተዳዳሪዎች እስከ አውራጃ ገዢዎችና የወረዳ አስተዳዳሪዎች የነበሩት አመራሮች አንዳንዶቹ አይ ትምህርት ያልነበራቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ውስን የቤተክህነት ትምህርት የነበራቸው በመሆናቸው በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ህብረተሰብአዊ ለውጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነና በሚያስተዳድሩበት አካባቢም እንዴት ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንደሚፈጠር ያልገባቸውና፣ ህዝቡም እንደህብረተሰብ በብዙ ሺህ ድሮች እንዲተሳሰር ለማድረግ ያላቸው ችሎታ አልቦ ነበር ማለት ይቻላል። በአዲስ አበባም የነበረው ዘመናዊ ቢሮክራሲ አብዛኛዎቹ ውጭ አገር ተምረው የመጡ ቢሆኑም ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ዕድገት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይህን ያህልም ያልተገነዘቡ፣ እንዴትስ ንጉሳዊዉ አገዛዝ ቀስ በቀስ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ እንዲችል መወሰድ ያለበትን የዕውቀትና የስልጣኔ ፈለግ በማሳየት አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደረጉት እንቅስቃሴ አልነበረም። ይህ ዘመናዊነት የሚመስል አገዛዝና የፍጆታ አጠቃቀም በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከዘመናዊነት የተገለለው ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በሁለት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ እንጂ ምንም የሚያገናኛቸው ህብረተሰብአዊ መተሳሰር አልነበረም። በዚህ ዐይነት እጅግ ዝብርቅርቁ በወጣ ሁኔታ ውስጥ ነው አዳዲስ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ የማያድሱ የአኗኗር ስልቶችና አነጋገሮች እየተፈጠሩና እየተለመዱ፣ እንዲያም ሲል የታዳጊው ትውልድ ጭንቅላት ውስጥ እየሰረሰሩ በመግባት አስተሳሳቡን ማኮላሸትና ድርጊቱን መወሰን የጀመሩት። እንደምገምተው ከሆነ፣ መሸወድ፣ አራዳነት፣ ጮሌነት… ወዘተ.የሚሉት ጽንሰ-ሃሳቦች ከህብረተሰብአችን የዕድገት መዘበራረቅ መጀመር ጋር አብረው ብቅ ያሉና እንደኖርምና እንደስልጣኔ መለኪያ ሆነው መወሰድ የቻሉት። ከፈላስፋና ከምሁር እንዲሁም ከሳይንቲስት ይልቅ አራዳ መሆን የሚከበርበት ሁኔታ የተፈጠረበትና ቀስ በቀስም አብዛኛውን ታዳጊ ትውልድ በማዳረስ ከቁም ነገር እንዲሸሽ በማድረግ ሙልጭልጭነት፣ ተንኮለኝነት፣ አጭበርባሪነትና ቀስ በቀስም ወደሰላይነት የሚያደርስ ሁኔታ በማዘጋጀት በራስ ከመተማመን ይልቅ የክህደት ጥንስስ ሊጣል የቻለው በ1950ዎቹ መግቢያ ላይ ነው። ይህ አዲስ የህሊና መዘበራረቅ ቀስ በቀስ በመስፋፋት ራሳቸውን ሸጠው የራሳቸውን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ለሚፈልጉ ኃይሎች ቦታ ያዘጋጀ ልዩ የህብረተሰብ ክስተት(Sociological Phenomen) ነው። በአጭሩ ለዛሬው የአገራችን ሁኔታ ተጠያቂው ሳይታወቅና ሳይታሰብ የተዘረጋው ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና ከዚህ ጋር ሰተት ብሎ የገባው የካፒታሊዝም ጎተትና ይህ ከፊዩዳሊዝም ጋር መዋሃዱ ልዩ ዐይነት አስተሳሰብ መፍጠሩ እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት የማርክሲዝም ርዕዮተ-ዓለም የፈጠረው ጉዳይ አይደለም ለዛሬው ሁኔታ ተጠያቂው። የማርክሲዝም አራማጆች ተጠያቂ የሚሆኑት የህብረተሰብአችንና በጊዜው የተፈጠረውን የህሊና አወቃቀር በደንብ ሳይመረምሩ የወሰዱት እርምጃና ስልጣን ለመያዝ መጣደፍና፣ ረጋ ካለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ህዝቡን ለውዠንብር የሚጋብዝ መፈክር ላይ መረባረቡ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን አድርጎታል። ስለሆነም ይህ የተዘበራረቀ ሁኔታና ዓለም አቀፋዊውን የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍና ተንኮል መሸረብ አለመገንዘብ ይበልጥ ለዛሬው የወያኔ አገዛዝና ለሻቢያ አመጸኛነትና አርቆ ያለማሰብ ትግል ቦታ እየሰጠ መጣ። እንደዚህ ዐይነት ተባዮች እንደ አሸን በመፍለቅና የነፃነት ተዋጊነት ስም ለራሳቸው በማጎናጸፍ ለዕውነተኛ ህብረተስብአዊ እንቀስቃሴ እንቅፋት ሆኑ። እነሱም የነባራዊውና የባህላችን ውጤቶች እንደመሆናቸው መጠን የማርክሲዝምን ካባ ቢከናነቡም የህብረተሰብአችን ምስቅልቅል ሁኔታዎች አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን በመወሰን ይበልጥ ተንኮልንና አመጸኛነትን አስቀደሙ። ለዕውነተኛ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ጥናት ቦታና ቅድሚያ መስጠት ተሳናቸው። እነዚህ እዚህም እዚያም ስልጣን ለመያዝ ከመሻኮትና ከመሸረብ አልፈው ሊሂዱ የማይችሉና ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት የሌላቸው ኃይሎች ከምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በመመሰጣጠርና ርዳታ በማግኘት ዕውነተኛ ብሄርተኝነትና ህብረተሰብአዊ ፍቅር እንዳይዳብር የእልክ ትግል ማካሄድ ቻሉ። እነ ውሃት ወይንም መሬዎቹ እነ አቶ መለስ እንደሚሉት በዕምነታቸው ማርክሲስት የነበሩ ሳይሆን፣ ማርከሲዝምን ሽፋን በማድረግ የተማሪውን እንቅስቃሴ በትኖ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ድጋፍ ስልጣን ለመያዝ የተጠነሰሰ ሴራ ነው። ለዚህም የተለያዩ ውስጣዊ ሁኔታዎችና በተለይም በስልጣን አካባቢ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ማነስና ርስ በርስ መጠራጠር ለወያኔና ሻብያ እንዲሁም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።

       በአጭሩ ለዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ የብዙ ነገሮች አንድ ላይ መጣመርና በተለይም ደግሞ በምሁሩ ዘንድ ሰፋ ያለ ንቃተ-ህሊናና ሁኔታውን አጥብቆ የመከታተል ጉዳይ ያለመኖርና ወገናዊንትን በማስቀደም አንዱ ሌላውን መቀናቀንና ለማጣፋት መታገል ለዛሬው አገዛዝ መንገዱን ቀዶለታል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ለሲአይ ኤ ሰላይ የሆነው የሚሊታሪና የሲቪል ቢሮክራሲ ኮሙኒዝምን እንታገላለን በማለቱና የወታደሩን አገዛዝ ለመጣል ባለው ያልተቆጠበ ትግል ምክንያት ለዛሬው አገዛዝ ሁኔታውን አመቻችቶ ሊሰጠው ችሏል። ምናልባትም ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ጋር ሲወዳደር በብዛት የሲአይ ኤና የሌሎች የምዕራብ የስለላ መረብ የተዘረጋበትና የሲቪልና የሚሊታሪውን ቢሮክራሲ ኮትኩቶ አገር የማፍረስ ሴራ የተካሄደበት እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ ደካማ አገር የለም ማለት ይቻላል። ኢትየጵያዊነትን ከማስቀደምና ለኢትዮጵያ ከመስራት ይልቅ የአሜሪካ ተላላኪ መሆን የተመረጠበትና ኢንፎርሜሽን በማቀበል ከፍተኛ የውንብድና ስራ የተሰራበት አገር ቢኖር ኢትዮጵያችን ነች። የዚህ ሁሉ ችግር አሁንም አርቆ አለማሰብና ጠለቅ ባለ ዕውቀት ጭንቅላትን ያለመገንባት ችግር ነው። ታላቁ ላይብኒዝ እንደሚያስተምረን እየተመራመርኩና እያወቅኹኝ በሄድኩ ቁጥር አገሬንና ህዝቤን የበለጠ እወዳለሁ ያለው በአገራችን ምድር በአዲሱ ቢሮክራሲ ጭንቅላትና ተማርኩ በሚለውና ዛሬም ስልጣን ላይ ቁጥጥ ባለው ጭንቅላት ውስጥ ሰርጎ ባለመግባቱ ለአገራችን ችግር ተከታዩ ምክንያት ሊሆን በቅቷል። አገዛዙ ከሚያካሂደው ማተራመስ ባሻገር ዛሬም በመሀከላችን ያለው ግራ መጋባት ይህንን ከላይ አጠር መጠን ባለ መንገድ የቀረበውን ሀተታ ለመረዳት ፍላጎት አለመኖር ወይም ያለመቻል ነው። የአንድን ህብረተሰብ ጉዞና እንቅፋቶች በጥቁርና በነጭ ለማየትና ለመጻፍ መሞከር ከአንድ ስህተት ወደሌላ እየመራን መቋጠሪያው እየጠፋን ነው።

       ከዚህ አጠር መጠን ያለ ትንተና ስነሳ የፕርፌሰር ሃይለማርያም ጽሁፎች እስከዚህም ድረስ ዕውነቱን ወደ መፈለግና ወደ ማግኘት የሚያመሩ አይደሉም ብል እንደ ውንጀላ አይቆጠርብኝም። የዛሬውን አገዛዝ ባህርይና ፖለቲካ ስልት ለመረዳት የያዘው የአጻጻፍ ስልት ግልጽ አይደለም። የህብረተሰብአችንን የታሪክና የህብረተሰብ ሂደት(Social and Historical Processes) በየታሪኩ የዕድገት ደረጃ እየነጣጠለ በመወሰድና በመመርመር ችግሩን ለመረዳት እንድንችል መንገዱን አያሳየንም። የዛሬውን አገዛዝ አምባገነን ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም። የባህሉንና የታሪክን ሜዳ ለመረዳት አንድ ርምጃ ቀደም ብሎ መሄድ ያስፈልጋል። የዛሬውን ሁኔታ ከትላንትናው ጋር በማያይዝ ምን ያህል ተሳሳቢነት እንዳላቸው በመረዳት ለወደፊቱ አዲስ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት እንደንተለም በቀጥታ ከምናያቸው ነገሮች አልፈን ለማየትና ለመመርመር መዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህን ሳይገነዘቡና ሳይመረምሩ ትንተና ለመስጠት መሞከር ለስልጣኔ የሚደረገውን ዕውነተኛና ሰፊ ምሁራዊ ትግል በእንጭጩ እንዲቀጭ ያደርጋል። ከዚህ ተነስቼ ደግሞ ለምን የምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም አሜሪካን የእነ አቶ መለስን አገዛዝ የሙጥኝ ብሎ እንደያዘና እንደሚረዳ ላመልክት።

  ወያኔና የምዕራቡ ዓለም በተለይም የአሜሪካን ፖለቲካ!

       ከዚህ ተነስተን ዛሬ የወያኔን ባህርይና የአገዛዝ ስልት እንዲሁም ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለውን መተሳሰር ለመግለጽ ስንሞክር አገዛዙ ካደገበት የማቴሪያልና የባህል እንዲሁም የአዕምሮ መቀረጽ ሁኔታ ነጥሎ ማየት በፍጹም ስህተት ነው። በተለይም የደርግ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ በአገራችን የተስፋፋ የአጻጻፍ ስልት አለ። እስከዚያ ድረስ ግን ሁሉም ማርክሲስት በነበረበት ዘመን በመደብ ጥያቄና ለአብዮቱ በቆሙና ባልቆሙ መሀከል አስተሳሰቦችን ለማስፋፋትና „የሶሻሊዝምን የበላይነት ለማረጋገጥ“ የሚደረግ ትግል ነበር። ስለዚህም ትንተናውም ሆነ አስተሳሰቡ ውስን የነበረና የሰውም የማሰብ ኃይል በተወሰኑ ጽንሰ-ሃሳቦች ዙሪያ የሚሽከረከርና ለጥበብና ለሌሎች የፈጠራ ስራዎች እንቅፋት የሆነ ሁኔታ ነበር። ሁሉም ጓድ መሆንና መባልን ይፈልግ ነበር። ከፍየል ወጠጤ ዘፈንነት የሚያስመልጠውም መንገድ ሳይወዱ ጓድ መሆንና ማርክሲስት መባል ነበር። ይህ የጨለማው ዘመን አልፎ የወያኔው ዘመን ሲመጣ የረቀቀ፣ የሰከነና የበሰለ የሚባሉ ከዚህም ከዚያም ተወስደው የሚጻፉ የአጻጻፍ ስልቶች ተስፋፍተው ነበር። እጅና እግር የሌላቸውና የሰውን አስተሳሰብ የሚያዘበራርቁና ከምን ተነስተን ወዴት መሄድ እንዳለብን ማሳየት የማይችሉ የአጻጻፍ ስልቶች። በተለይም በጦቢያ መጽሄት ላይ የሚስተጋባው የአጻጻፍ ስልት ይህንን ይመስል ነበር። ይሁንና ግን ለሁሉም ዐይነት ጸሀፊ የአገራችን ሁኔታ አስቸጋሪን ነገር ፈጥሯል። ዓለም ወደ አንድ አቅጣጫ እያመራች ነው። ዘመኑ ዘመነ-ሶሻሊዝም አክትሞ የነጻ ገበያ የሚወደስበት ዘመን ነበር። የዓለምም ፖለቲካ በሁለት ኃያላን መንግስታት የሚወሰንበት ጊዜ መሆኑ ቀርቶ በአንድ ኃያል መንግስት ወደ መወሰን የሚያመራ ነበር። ስለዚህም የወያኔ አገዛዝም በአንድ ኃያል መንግስት እየተዋቀረ የመጣውን የገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍናና የፖለቲካ ስልት አምኖም ይሁን ተገዶ የሚቀበልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ስለዚህም አገዛዙ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አሜሪካን ጉያ ውስጥ ገብቷል። በሌላ ወገን ግን ወያኔንም ሆነ የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ የሚቃወመው ይህንን ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ኃይል አስላለፍ ለውጥና በአገራችን ላይ ሊኖር የሚችለውን ተጽዕኖ ለመመልከት እንዳሰቸገረው በተለይም በመጀመሪያዎቹ አስር ዐመታት ይታተሙ የነበሩትን መጽሄቶች ላገላበጠ ሊገነዘበው ይችላል። አገዛዙ በራሱ ኃይል ቆሞ የሚራምድና የኢትዮጵያን ህልውና የሚወስን ወይም ደግሞ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በተለይም ከአሜሪካን ጋር በሺህ ድሮች በመተሳሰር የአገራችንን ህልውና የሚውስን ነው ብሉ ሳይንሳዊ ትንተና ለመስጠት የተሳነው ወይም ደገሞ የነገሮችን ሂደት ማየት የማይችል ነበር። ይህ የተዘበራረቀ ሁኔታና በተለይም ጸሀፊ ነኝ የሚለው የሚያስፋፋው ብዙም ተጨባጭ ሁኔታዎችን በዲያሌክቲክ መነጽር እንድንገመግም ለማድረግ የማያስችል ሁኔታ ለወያኔ አገዛዝ መጠናከርና ለአሜሪካን የበላይነትና በተለያዩ መሳሪያዎች አማካይነት የአገራችንን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ህልውና እንዲወስን አድርጎታል። በአገራችን ምድር አዲስ የኃይል አስላለፍና የሀብት ክፍፍል ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ ድህነትና የመንፈስ አቅመ-ቢስነት ሊስፋፉና ሊጠናከሩ ችለዋል። ከዚህ ስንነሳ በአንድ ሰሞን ማርክሲስት ነኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይል የነበረው የነጻ አውጭ እንቅስቃሴ በአንድ ጊዜ መቶ ሰማንያ ዲግሪ ተቀልብሶ ለምን ኢምፔሪያሊስት ነው እያለ ሲሰድብ በነበረው መንግስት ጉያ ውስጥ ገብቶ ለመንደፋደፍ በቃ?

     በአብዛኛው በኛ የኢትዮጵያ ምሁሮች ዘንድ የምዕራቡን ዓለም የውስጥም ሆነ የውጭ የፖለቲካ ለመረዳት ችግር እንዳለብን ከሚወጡት ጽሁፎች በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል። በምዕራቡ ዓለም አሜሪካንንም ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች መኖርና በነጻ መወዳደር፣ እንዲሁም የህግ የበላይነት የሰፈነበትና ሰብአዊ መብት የተከበረበት ነው የሚሉት አነጋገሮች በእርግጥም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በተግባር የሚታዩት የምዕራቡን ፖለቲካ ጠለቅ ብለን ለመመርመር እንዳንችል ከመጀመሪያውኑ ውስን አስተሳሰብ ውስጥ ጥለውናል። በሌላ ወገን ደግሞ ለየት ያለ ትንተናና ገለጻ ለመስጠት የሚሞክሩትን በማስፈራራትና የተለያዩ ቅጽል ስሞች፣ ኮሙኒስት፣ ራዲካል፣ አክራሪና ማርክሲስት እያሉ ስም በመስጠትና የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ ጤናማና ለህብረተሰብአችን የሚጠቅም ውይይት ማካሄድ በፍጹም እንዳይቻል ተደርጓል። በተጨማሪም ክርክር እንዳይደረግ ጥቂት ግለሰቦችን ተገንና እነሱን ብቻ አዋቂ አድርጎ ሌሎችን በማንቋሸሽና በማግለል የተሰራውና የሚሰራው የጮሌዎችና የስልጣን ፈላጊዎች ወንጀል ሳይንሳዊና ለስልጣኔ የሚሆን ጤናማ ውይይት እንዳይካሄድ በሩን ሁሉ ዘግቷል። ባጭሩ የተገዢነትና የሽንፈት ባህርይ በማዳበርና ታዳጊው ትውልድ ለአገሩ አውቆና ነቅቶ እንዳይታገል እንቅፋት በመሆንና የማይሆን ትንተና በመስጠት ሀቁ እንዳይታወቅ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ጨለማን ሁኔታ እየፈጠርን ነው። የዚህ ጸሀፊ አላማና ዕምነት ነገሮችን በጥቁርና በነጭ እየለዩ በማየትና በመጻፍ „አክራሪነትን“ ለማስፋፋት አይደለም። ወይም ኢምፔሪያሊዝም እያልን ወደማይሆን ግብ ግብ ውስጥ በመግባት ትግሉን ውስብስብ ለማድረግ አይደለም። የኔ ዕምነትና ፍላጎት በግልጽ እንነጋገር ነው። በታሪክ እንደታየውና ላይም ለማብራራት እንደሞከርኩት የምዕራቡ ስልጣኔ በክርክር ላይ የተመሰረተ ነው። በመጀመሪያ በሃሳብ ዙሪያ የሚደረግ ክርክር ነበር የምሁሮችን አስተሳሰብ ለመሰብሰብ የቻለው። ስለዚህም በዚህ ጸሀፊ ዕምነት ዕውነትን ከመናገር ይልቅ ዕውነቱን መፈለግ ማስቀደም አለብን ነው። ዕውነት ናቸው በሚባሉ መሀከልም ልዩነት እንዳለ መገንዘብ እንዳለብን ነው። በሌላ አነጋገር አንዱ ዕውነት ነው በሚለውና ሌላው ዕውነት ነው በሚለው መሀከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ለማስገንዘብ ነው። የተለያዩ ምሁሮችና ፈላስፋዎች ይህችን ዓለም በተለያየ መልክ ተርጉመዋታል፤ እየተረጎሟትም ነው። ስለዚህም ለእኛ ኢትዮጵያውያን፣ የተለያዩ ምሁሮች የአገራችንና የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ በተለያየ መልክ ቢተረጉሙት መገረም የለብንም። ወይንም እንደ ቅዠትም መቁጠር የለብንም። ታሪክ የመጨረሻዋን ፍርድ አልሰጠችም። ስለዚህም ዛሬ የምናያትን ዓለም እንደታሪክ መደምደሚያ አድርገን መቁጠር የለብንም። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ደግሞ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ይቃወማል። እንደዚህ ብለን የማንስብ ከሆነ ደግሞ ህብረተሰቦችም ሆነ የዓለም ፖለቲካ የራሳቸው ውስጣዊ ህግና ውስጠ-ኃይል የላቸውም ብሎ አምኖ እንደመቀበል ይቆጠራል። በመሆኑም ዕድገት አይኖርም ማለት ነው። አንድ ቦታ ላይ ከደረሰ በኋላ ሁሉም ነገር እዚያው ይቀራል ማለት ነው። ስለዚህ ከውስን አስተሳሰብ መላቀቅ የምሁሮች ዕምነት መሆን አለበት።

     በአጠቃላይ ሲታይ በምዕራቡ ዓለም ዲሞክራሲ አለ ስለተባለ ሰለጠን የሚሉት መንግስታት ለዓለም ማህበረሰብ ሰብአዊ መብትና የኢኮኖሚ ዕድገት እንደቆሙ አድርጎ መቁጠር ትልቅ የታሪክ ወንጀል እንደመፈጸም መቁጠር ነው። የየአገሮቻውን ጥቅም በቅድሚያ እንደሚያስቀድሙና በተወሰነ የፖለቲካ ሎጂክም እንደማይመሩ አድርጎ መቁጠሩ ትልቅ ስህተት ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል። ይህ ብቻ አይደለም፤ በዲሞክራሲ ስምና ኮሙኒዝምን ለመዋጋት በሚል ሽፋን ስር ባለፈው ስድሳ ዐመት በየዋህ ህዝቦች ላይ የተፈጸመውን ዐይን ያወጣ ወንጀል ቁጥር ውስጥ አለማስገባት እኛንም እንደ ወንጀለኞች ያስቆጥረናል። ያም ሆነ ይህ በሁሉም የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና አሜሪካንም ጨምሮ  በካፒታሊዝም ሎጂክ ላይ የተመሰረተ ግልጽ የሆነ የስራና የሀብት ክፍፍል አለ። በተጨባጭ ሲታይ መንግስታትና ፓርቲዎች ይህንን የሀብትና የስራ ክፍፍል የሚጠበቁና የሚያስተዳድሩ ናቸው። ባለፉት ስድሳ ዐመታት በሰራተኛው የሙያ ማህበር የተደራጀው ስራተኛ በትግል የመደራደር መብት ቢያገኝም በመንግስቱ መኪናና በፓርቲ ፖሊሲ ላይ የሚያደርገው ተጽዕኖ በጣም ውስን ነው። በተለይም ከሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ዐመታት ጀምሮ የኒዎ-ሊበራሊዝም ርዕዮተ-ዓለም የበላይነትን እየተቀዳጀ በመምጣቱ በተጨባጭ ሲታይ በተለያየ ስም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ይህንን ርዕዮተ-ዓለም እንዲቀበሉ ተገደዋል። የመንግስትን ሀብት መሸጥ፣ ሁሉንም የኢኮኖሚ ክንውን ከትርፍ አንጻር መመልከትና ከምርታማ ተግባር ይልቅ ቶሎ ቶሎ ትርፍ ወደሚያመጣ የአየር ባየር(Speculation) ንግድ ላይ ማተኮር፣ ወደ ወስጥ የኃይል አስላለፍ ለውጥ ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን የመንግስታት ሚና ወደ ረቀቀ የዜግነትን መብት ወደሚገፍ ፖለቲካ እንዲሸጋገሩ አስገድዷቸዋል። በአብዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ አገሮች፣ አማሪካን፣ ጀርመን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ የሀብት ሽግሽግ ይታያል። ባለፉት ሃያ ዐመታት በሞኔታሪዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመደገፍና ለሀብታሙ የቀረጥ ቅነሳ በማድረግ መንግስታትና ፓርቲዎች ከዌልፈር ስቴት ሚናቸው እያፈነገጡ መጥተዋል። በዚህም ምክንያት በደሀና በሀብታም መሀከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል። በጀርመንም ሆነ በአሜሪካ ከ2-5% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ከ80% በላይ የሚሆነውን ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆነ ሀብት ይቆጣጠራል። ስለሆነም በሀብታሞችና በደሀ መሀከል ከፍተኛ የገቢ ልዩነት ይታያል። በተለይም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችንና ባንኮችን እንዲሁም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመንግስታት ፖሊስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር እየተሳሰሩ መጥተዋል። የዓለምን የጥሬ ሀብት የሚቆጣጠሩ ኢንቬስትሜንት ባንክ የሚባሉት መንግስቶቻቸው ወደ ውጭ ጥቅም አስጠባቂ እንዲሆኑላቸው አድርገዋል። የኢንዱስትሪዎች በትላልቅ ባንኮች ቁጥጥር ስር መውድቅና መተሳሰር፣ እነዚህ ደግሞ በመንግስታት ፖሊሲ ላይ ጫና ማድረግ የየመንግስታቱን የውስጥም ሆነ የውጭ ፖሊሲ በነሱ ሎጂክ እንዲመራ ለማድረግ ተችሏል። በሌላ አነጋገር የምዕራብ መንግስታት አሜሪካንንም ጨምሮ ፕሬዚደንቶችና ጠቅላይ ሚነስተሮች በፖለቲካ ውሳኔያቸው ነፃና ህገ-መንግስቶቻቸውን ተክተለው የሚመሩ አይደሉም። በተጨማሪም አዲሱ የፖለቲካ ኤሊት እንደ ሃምሳዎቹ፣ ስድሳዎቹና ሰባዎቹ ዐመታት ዐይነት መሬዎች ሳይሆን በጥቅም የተገዛና የተሳሰረ በመሆኑ የየህብረተሰቦችን ሂደት እያጣመመና ተዋጊ መደብ(Warrior Class) በመሆን የዩሊታሪያኒዝምን ፍልስፍና እያስፋፋ የመጣ ነው። በተለይም ቴሮሪዝምን እንዋጋለን በሚል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰው እንቅስቃሴና የኢንፎርሜሽን ልውውጥ ሁሉ እየተሰበሰበና እየተከማቸ ህዝብን መሰለያና መጠባበቂያ ሆኗል። በየአገሮች የስለላ ድርጅቶች ሙሉ መብት በማግኘትና ከፓርሊሜንታሪ ቁጥጥር ውጭ በመስራት ራሳቸውን የቻሉ ኢንስቲቱሸኖች ሆነዋል። በአሜሪካ 20 የስለላ ድርጅቶች አሉ። ሲአይ ኤ ብቻ ወደ ስምንት መቶ ሺህ የሚጠጋ ሰራተኞች አሉት። የኦባማ አስተዳደር ይህንን ለመቆጣጠር የራስ ምታት ሆኖበታል። ዛሬ በተለይም ዋና ዋና በሚባሉ የካፒታሊስት አገሮች ስርዓቱን የሚቆጣጠረው የሚሊታሪና የኢንዱስትሪ ውስብስብ(Military-Industruial Complex) የሚባለው ነው። ይህንን ለመረዳት ታሪክን ወደ ኋላ ዞር ብሎ መመልከት ያስፈልጋል።

       ይህ የሚሊታሪና የኢንዱስትሪ በመንግስት መኪና ላይ ቀስ በቀስ እያለ ያሳርፍ የነበረውን ተጽኖ የተለያዩ የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች እንዴት በጭንቀት ይመለከቱት እንደነበር  ዕውነተኛ ከሆነው አነጋገራቸው እንስማ። „Over-grown military establishments are under any form of government inauspicious to liberity, and are to be regarded as particularly hostile to republican liberity.“ – George Washington (1732-1799), 1st US President  በተጨማሪም ፕሬዚደንት አይዘንሀወር ስጋታቸውን እንደዚህ በማለት ይገልጻሉ። “[The] conjunction of an immense military establishment and a large arms industry is new in the American experience…. In the councils of government, we must guard against the acquisition of unwarranted influence, whether sought or unsought, by the military-industrial complex. The potential for the disastrous rise of misplaced power exists and will persist.” –Dwight D. Eisenhower(1890-1969), 34th US President, Farewell Address, Jan. 17, 1961 ቀጥሎም ሌላው ይህ ልቅ ሁኔታ ያሳሰባቸው ጄኔራል እንደዚህ ብለው ይናገራሉ። “It is part of the general pattern of misguided policy that our country is now geared to an arms economy which was bred in an artificially induced psychosis of war hysteria and nurtured upon an incessant propaganda of fear.” — General Douglas MacArthur, Speech, May 15, 1951) ይህ ሁኔታ በቡሽና የቼኒ አስተዳደር ዘመን እየጠነከረና ኢኮኖሚው የበለጠ በጦር አኮኖሚ ቁጥጥር ስር እንዲመጣ ሊያደርገው በቅቷል። በፕሬዚደንት ሬገን የግዛት ዘመን በጊዜው ሶቭየት ህብረትን ለማዳከም በሚሊታሪ-ኬኔዚያኒዝም የሚደገፈው የተወሳሰበ በኤሌክትሮኒክና በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተው የጦር መሳሪያ ምርት በነ ፕሬዚደንት ቡሽና ቼኒ አገዛዝ ዘመን የባሰ ጥልቀትንና ስፋት አገኘ። ሪፓብሊካኖች ባደረጉት የውስጥ ኩዴታ ህዝቡን ለማስፈራራትና የጦር መሳሪያ ባጀትን በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ዕደል አገኙ። አሜሪካ አደገኛ ቦታ ላይ ወድቃለች በማለት ዓለምን ለማሰስ በህዝቡ ዘንድ ፍርሃትን አስፋፉ። በዘመነ ግሎባለይዜሽን ይህ ሁኔታ በመጧጧፍ አሁን ደግሞ የጥሬ ሀብትን መቆጣጠር አለብን፣ ቻይና ቀደመችን እያሉ ደካማ የአፍሪቃ መንግስታትን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ሽር ጉድ እያሉ ነው። የኦባማ አስተዳደርና በምዕራብ አውሮፓ በየጊዜው እየተፈራረቁ የሚገዙ የተለያየ ስም ያላቸው ፓርቲዎች በመሰረቱ ከዚህ በተለይም ባለፈው ሃያ ዐመት እየጠነከረ ከመጣው የኃይል አሰላለፍ ቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። ዛሬ ስር ሰዶና የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠርና በየጊዜው የሚመረጡትም ፕሬዚደንቶች ምክንያቶች እየፈጠሩ ወይም እየተፈጠረባቸው ጦርነት የሚያካሂዱት አንዳንዶች ለማሳመን እንደሚሞክሩት የአሜሪካን የውስጥም ሆነ የውጭ ፖለቲካ በፕሬዚደንቶች የሚወሰን እንዳልሆነ ነው። በኢራቅና በአፍጋኒስታን ህዝቦች ላይም የሚወርደው ቦንብና የሚደርሰው የህዝብ ዕልቂት ይህ የሚሊተሪና የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ከሚከተለው ዓለም አቀፋዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ተነጥሎ መታየት የለበትም። መሳሪያዎች በየጊዜው መፈተን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ጦርነት ልክ እንደ ዕቃ ወደኛ ላሉ ምስኪን ህዝቦች ዘንድ ኤክስፖርት መደረግ አለበት። ስለዚህም የቴሮሪዝም ጉዳይ ሽፋን እንጂ የጦርነቱ መነሻ አይደለም። በዚህም ምክንያት እነዚህ በቴሮሪዝም ስም አሳበው ጦርነት ያወጁ የምዕራብ መንግስታት ለኢትዮጵያ የተለዩ ርህሩህ ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህ አጠቃላይ የውጭ ፖለቲካቸው የሚያዘናጋቸው አንዳችም ነገር የለም። ይህንን መካድ ወይም ላለመቀበል መፈለግ የዓለምን የፖለቲካ ሎጂክና አረማመድ ለመረዳት ያለመቻል ወይም አለመፈለግ ነው።

       ከዚህ አጠር ካለ ሁኔታ ነው የአሜሪካንን የውጭ ፖለቲካና ከወያኔ ጋር ያለውን ግኑኝነት መረዳት የሚቻለው። የአሜሪካን መንግስት ለአገሩ ህዝብ ደህንነት ጠበቃ ያልሆነውን ያህል ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠበቃ ሊሆን አይችልም። አሜሪካን ለዓለም ህዝቦች የሰብአዊ መብት የቆመ ነው ብለን የምናምን ከሆነ አሜሪካን ውስጥ ምን እንደሚሄድ አናውቅም ማለት ነው። ራሱ አብዛኛው የአሜሪካ ህዝብ እንኳ በአገሩ ውስጥ ምን እንደሚካሄድ የማያውቅበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ሁኔታዎችን የሚከታተል መገንዘብ ይችላል። እንኳን በአገር ደረጃ ቀርቶ በአንድ ከተማ ውስጥ ቀን ተቀን የሚካሄደውን የማያውቀው ብዙ ነው። ይህንን በአንድ ምሳሌ ላሳይ። ሎስ ኤንጀለስ እስር ቤት የነበሩ በወንጀል የታሰሩ ከተፈቱ በኋላ ስራዬ ብለው የያዙት የቱሪስት መሪ በመሆን በከተማይቱ ውስጥ ምን እንደሚካሄድ በአውቶቡስ ለኑዋሪው ህዝብ ማሳየት ነበር። የከተማይቱን አንዳንድ ኑዋሪ ሰዎች ወንጀለኞችና የድረግ ሱሰኞች ወዳሉበት ወደ ቆሸሸ ቦታ እያዘዋወሩ ሰው እንዴት እንደሚኖር ለዚያው ኑዋሪ ቱሪስት ያሳይዋቸዋል። ሰዎችም በሄዱበት ቦታ በሙሉ የሱሰኛውን ሁኔታና የቦታውን መቆሸሽ እየተመለከቱ እዚህ ከተማ ስኖር ወደ አርባ ዐመት ይጠጋኛል፤ ይህንን አካባቢ በፍጹም አላውቀውም የሚል ነበር መልሱ።  ይህ ዘገባ በናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ ተጠናቅሮ የቀረበ ነበር። ባጭሩ የአሜሪካንን የውስጥ ፖለቲካ ለመረዳትም ሆነ ለመገንዘብ ፍላጎት እስከሌለን ድረስ ውጭ የሚያካሂደውንም መረዳት አንችልም። ይህንን ካልተገነዘብን ደግሞ በወያኔና በአሜሪካ መሀከል ያለውን የእከክልኝ ልከክልህ ፖለቲካ መገንዘብ አንችልም። ስለዚህም ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት እንታገላለን የምንለው በሳይንስ ላይ ባልተሰመሰረተ ጥናት ተመርኩዘን ነው ማለት ነው።

       ስለዚህ የምዕራብ አውሮፓንም ሆነ የአሜሪካንን የውጭ ፖለቲካ እኛ እንደምንመኘው በመትወትወት እናስቀይረዋለን ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ  የበላይነትን(Hgemony) ለመቀዳጀት የሚካሄደውን ትግል አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሞኝነት ነው። አንዳንዶቹ እንደሚሉት እኛ “ የሰከነ የዲፕሎማሲ ትግል”  ስላካሄድን ወይም አንገታችንን እየደፋን ስለምንቀርባቸው ርህራሄ በማሳየት እንደምትፈልጉት እናደርግላችኋለን ብለው ወያኔን የዐይን ላፈር ሊሉት አይችሉም። በሌላ ወገን ግን ይህ የዲፕሎማሲ ትግል መካሄድ አለበት እያለ የሚወተውተው ታጋይ ዲፕሎማሲ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ዲሞክራሲንና የኢኮኖሚ ዕድገትን እንዲሁም ብሄራዊ ነጻነትን ከውጭ ኃይል ጋር ተቀምጦ በድርድር ወደ አንዳች ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ወይ? ወይስ የዲፕሎማሲ ትግል ሲባል ከወያኔ ይልቅ እኛ አሸባሪ ኃይሎችን መዋጋት እንችላለን፤ ዋናው ቁም ነገር በእናንተ ርዳታ ስልጣን ላይ ብቻ እንውጣ ለማለት ታስቦ ነው?   ለማንኛውም ፕሬዚደንት ኦባማ ከተመረጠ በኋላ የዓለም ህዝብ የአሜሪካን የውጭ ፖለቲካ መሰረታዊ ለውጥ ያሳያል ብሎ ገምቶ ነበር። በአቀራረብና በድምጽ ካልሆነ በስተቀር መሰረታዊ ይዘቱ በፍጹም አልተቀየረም። የፕሬዚደንት ኦባማም መመረጥ ካለምክንያት አይደለም። ለጊዜውም ቢሆን የሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ እነ ቡሽ-ቼኔ በአሜሪካ ላይ ያደረሱትን ዓለም አቀፋዊ ጥላቻ ለዘብ የሚያደርግለት ፕሬዚደንት ይፈልጋል። ለአራት ወይም ለስምንት ዐመታት የዓለም ህዝብ በአሜሪካ ላይ ያለውን አመለካከት ሊለውጥ ይችላል ብሎ ይገምታል። ከስምንት ዐመት በኋላ ደግሞ ሌላ አቅራሪ ኃይል በመምጣት የአሜሪካንን የበላይነት ለማረጋገጥ ወደ ሌላ ጦርነት ሊሄድ የሚችልበትን ሁኔታ ያመቻቻል።  በአጭሩ የፖለቲካው ጨዋታ ይህንን ይመስላል።

       ከዚህ በተረፈ ዓለምና የዓለም ገበያ የውድድር መድረክ መሆናቸውን መገንዘብ አለብን። የዓለም ገበያ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። በአንድ በኩል የሞኖፖሊ ጨዋታ የሚካሄድበት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህ አላዋጣ ሲል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህንን ካልተቀበልክ እየተባለ ጦርነት የሚካሄድበት መድረክ ነው። እንደ ራሺያ፣ ቻይናና ህንድ የመሳሰሉ ካልሆነ በስተቀር ይህንን የምዕራቦችን የሞኖፖሊ ጨዋታና ማስፈራሪያ ፖለቲካ እንደ ወያኔ የመሰሉ መንግስታት እንደቡራኬ ነው የሚቀበሉት። በሌላ በኩልም አሜሪካንም ሆነ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት ሶቭየት ህብረት ከፈረሰች በኋላ ራሺያን ከበው ለማዳከምና ሀብቷን ለመዝረፍ ያላደረጉት ሙከራ ይህ ነው አይባልም። ልፍስፍሱ የዬልሲን መንግስትና በፕሮፌሰር ጄፈርሲ ሳክስ ይመከር የነበረው አዲሱ የራሺያ ኤሊት ራሺያን ለምዕራቡ አጋልጦ ከሰጠ በኋላ ነው በፕሬዚደንት ፑቲን አማካይነት ልታገግምና ልትድን የቻለቸው።  እንደ ኢትዮጵያ ያሉት በደካማ የውስጥ አገዛዝ የታገዙ አገዛዞች  ግን ሰጥ ለጥ ብለው ከመገዛትና ድህነትን ከማስፋፋት ሌላ አማራጭ የሌላቸው ብቻ ሳይሆን፣ አገዛዞቹ ራሳቸው በአነሳሳቸው ለዚህ ውድቀት የተዘጋጁ ናቸው። ስለዚህም በወያኔ አገዛዝና በአሜሪካን መሀከል የመተሳሰርና ህዝብን የማድኸየት፣ እንዲሁም የጦርነት ፖሊሲ መሀከል ልዩነት የለም። የምዕራቡ ዓለም እንደወያኔ የመሰለውን አገዛዝ ተገን በማድረግና በመደገፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣኔ እንዳይመጣ የማይሸርበው ተንኮል ይህ ነው አይባልም። በመሆኑም ስለወያኔ አምባገነንነት ስናወራ ከዚህ የምዕራቡ የተበላሸ ዓለምን የጦር አውድማ ከማድረግ ፖለቲካ ነጥለን ማየት አንችልም። ባጭሩ ለህዝባችንና ለአካባቢው ወንድማችን የሶማሌ ህዝብ ተጠያቄ ወያኔ ብቻ ሳይሆን እኛም ምሁር ነን ባዮች ነን። ዓለምን በራሳችን ሎጂክ በመቅረጽና የሚሆን የማይሆን ትንተና በመስጠት ታዳጊውን ወጣትና ህዝባችንን የማሳሳት መብት የለንም። ከዚህ ውዥንብር መላቀቅና የጠራና በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመረኮዘ ትንተና መስጠቱ የታሪክና የሞራል ሃላፊነት ነው። ምክንያቱም አደባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነውና!

ዋናው ችግራችን ! ሃቁን መፈለግና መናገር ያለመቻል !

                   “The last man whose image Zarathustra flings at the people is the antithesis of the

                       superman and therefore, like the superman, an extreme. Whereas the superman

                       symbolizes the transcendence of the human condition, the last man is marked

                       by the absence of higher aspirations; he is little more than a well-fed and self-

                       satisfied beast. Incapable of imaging, much less striving for worthy goals, the

                       last man is almost subhuman because he is numb to wonder and shame alike”.

                      (Peter Berkowitz, Nietzsche: The Ethics of an Immoralist, London 1995,P. 142)

            የምዕራቡ ዓለም አሜሪካንም ጨምሮ እንደዚህ አደረገን፣ ወይንም ከጎናችን አልቆመም ብለን ስንወነጅለው በራሳችን አቅም ራሳችንን ነፃ ለማውጣት ብቃት እንደሌለንና አቅም እንደተሳነን ነው የምናረጋግጠው። የምግብ ዕጥረት ሲኖርንና ረሃብ ሲከሰት የምንጮኸው የምዕራቡ ዓለም ካልደረሰልን እያልን ነው። ለአንድ አገር ዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም እንደህብረተሰብ በሺህ ድሮች መተሳሰር የመቻልና ያለመቻል ጉዳይ ኃላፊነቱ በራሳችን እንደሚወሰን ከዘነጋን ዘመናት አልፎናል። ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት ተሰምቶን ራሳችንን በራሳችንን ነጻ ለማውጣት የምናደርገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሽንፈት መንፈስ በጭንቅላታችን ውስጥ አሳድረናል። የውጭ ኃይል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የአንድ አገር አገዛዝና ምሁር በሚከተለው የነቃ ፖለቲካ ብቻ መሆኑን ልንገነዘብ አልቻልንም። የውጭ ኃይል አስተዋጽኦም ውስን ሚናን ሊጫወት እንደሚችል ብቻ የስልጣኔን የታሪክ ማህደር ላገላበጠ ሊረዳ ይችላል። ዋናው መሰረተ-ሃሳብ፣ አንድ በተለይም እንደኛ ያለ የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ አለን የሚል ህዝብ አሁንም በድህነትና በረሃብ ሲጠቃና ለማኝ ሆኖ ሲቀር ምክንያቱን ለማወቅ መጣጣር ያለበት ህዝቡና ምሁሩ ብቻ ነው። ጥያቄ የማይጠይቅ፣ ችግሮች ሲከሰቱ እነሱን ለመቅረፍ የማይችል ከሆነ፣ በተለይም በዚህም በዚያም ብሎ የሚሆን የማይሆን ምክንያት የሚሰጥ ከሆነና ችግሩን በሌላው ላይ የሚያሳብብ ከሆነ እንደዚህ ዐይነት ህዝብ ታሪክን ለመስራት አይችልም። ታላላቅ ነገሮችን እየገነባ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ አይችልም ማለት ነው። የኛ ትልቁ ችግር እንደሰው መኖራችንን ለመገንዘብ ያለመቻል ነው። እንደ ሰው ሆኖ መፈጠሩን ያልተገነዘበና ራሱንና አካባቢውን ለመለወጥ የማይችል ህዝብ ደግሞ በቀላሉ በውጭ ኃይሎች ይጠቃል። ወደ ባርነት እንዲቀየር ይደረጋል። ዛሬ በአገራችን ምድር የምናየው ይህንን ሀቅ ነው። ወደ ባርነት መገፍተሩ ግን በቀጥታ የምናየው ነገር አይደለም። የውጭ ኃይሎች ያስቀመጡት በሚመስልና በሚንከባከቡት አገዛዝ የሚካሄድ ተዘዋዋሪ ዘረፋ ነው። አሁን በምናካሂደው የትግል ስልትና ንቃተ-ህሊና ሊታይ የሚችል ጉዳይ አይደለም።

       ስለ አገራችን ወደ ኋላ መቅረት እስካሁን ድረስ ምሁር ነኝ በሚለው የሰከነና ጠለቅ ያለ ጥናት ቀርቦ አይካሄድም። አብዛኛዎቻችን የስልጣኔንና የባህልን ዕድገት በገበያ ኢኮኖሚና በሊበራል ዲሞክራሲ ክልል ውስጥ በማስቀመጥ ሰፋ ያለና ለስልጣኔ የሚያመች ውይይት እንዳይካሄድ መንገዱን ሁሉ ዘግተናል። ስለዚህ ዛራቱስትራ እንዳለው በትንሽ ነገር ለመርካትና እጃችንን አጣጥፈን ለመቀመጥ የምንራወጥ እንጂ በሰፊውና ከረዢም ጊዜ አንፃር በማሰብና በመተለም ታሪክን ለመስራት የተዘጋጀን አይደለንም። ይህ ችግር ከምን የመነጨ ነው ? ከላይ እንደዘረዘርኩትና አንዳንድ ቦታም ለማሳየት እንደሞከርኩት የኛው ዋናው ችግር ፕላቶ እንደሚለው ጭንቅላታችንን ወደ ውስጥ ለማንበብ ያለመቻል ነው። ሌላ ምን አደረገ ከማለት ይልቅ እኔ ምን አስተዋፅኦ አበረከትኩኝ? ብለን ለመጠየቅ ያለመቻል ነው። የኛ ችግር በየጊዜው የምንሰራውን ስራ ለመመርመር ያለመቻል ነው። የተወሰኑ ርዕዮተ-ዓለሞችን ይዞ የሙጥኝ በማለት ለሌላ አስተሳሰብ ጭንቅላታችንን ክፍት እንዳናደርግ በሩን ዘግተናል። ዛሬ አንዳንዶች እንደሚሉት የሚካሄደው ትግል ማርክሲስት ነን በሚሉና ነፃ ገበያን ወይም ሊበራል ዲሞክራሲን እንፈልጋለን በሚሉ መሀከል አይደለም። የኛ መሰረታዊ ችግር የሃሳብን የበላይነት ለመረዳትና ለማስቀደም ያለመቻል ነው። በምናያቸው ነገሮች ላይ ብቻ በመረባረብ ጠለቅ ላለ አስተሳሰብ ክፍት ቦታ ለመስጠት ያለመቻል ነው።

       በድፍረት ልናገርና እንደ ዕውነቱ ከሆነ የስልጣኔው ቁልፍ ጠፍቶብናል። እኛ ብቻ አይደለንም። ጠቅላላው የአፍሪቃ ህዝብ ጭንቅላቱ የተዳፈነ ነው የሚመስለው። እንደከብት ለመነዳት የተዘጋጀ የሚመስል እንጂ በራሱ ጥረት መንፈሳዊ ኃይሉን ለማንቀሳቀስ ደፋ ቀና የሚል አይደለም። በትክክለኛው የዕውቀት ወይም የጥበብ ብርሃን ዐለማችንን ተረድተን ራሳችንን ለውጠን አገራችንን ለመገንባት ካልቻልን ዛሬም እንደትላንትናው ተበታትነንና የማንም መሳቂያ ሆነን እንቀራለን። ዛሬ በአገራችን ያለው አገዛዝ የኛው አንድ አካል ነው። ከኛ የሚለየው ጎጠኛና እልከኛ መሆኑ ነው። መቶ በመቶ በራሱ ዓለም ውስጥ የሚሽከረከርና ሀብትና ስልጣን ያሰከረው እንደቀትር እባብ የሚንቀጀቀጅና ይቀናቀነኛል ብሎ የሚገምትውን በሙሉ ለመንደፍ የተዘጋጀ ነው። ራሱን መጠየቅና ከስህተቱ ለመማር የማይችል ነው። የኛ ችግር ደግሞ ራሳችን የፈለቅንበትን ህብረተሰብ ለመገንዘብ ያለመቻል ነው። አገዛዙ ከ19ኝ ዐመት ዠምሮ የሚከተለው ፖለቲካ ከሌላ ዓለም እንደመጣ እንደሚያስመስለው ነው የምንገነዘበው ነው። የዛሬው አገዛዝም ችግር የኛም ችግር ነው። እኛም እንደሱ ራሳችን በሳልነው ዓለም ውስጥ የምንገኝ እንጂ በሳይንስ የተፈተነን ቲዎሪን መመሪያ በማድረግ አይደለም። ዕውነቱን ወይንም ሀቀኛውን መንገድ ለመፈለግ የያዝነው መንገድ ወደ ስልጣኔና ነጻነት አያመራንም።

       ከዚህ ችግር ለመላቀቅ እስካሁን የምንመራበትን የትግል ስልትና ቲዎሪ ርግፍ አድርገን መጣል አለብን። ለስልጣኔና ሁለንታዊ ለሆነ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ ሊያገለግል የማይመች መሆኑን ተገንዝበን ወደ ተሻለና ራስን ወደሚሰበስብና ዕውነትም እንደ ሰው ታሪክ ወደሚያሰራን የትግልት ስልት መሸጋገር አለብን። ስለዚህ ጥቃቅን አርቲክሎች ከመጻፍ ወደ ሌላ ችግርን ሊፈታ ወደሚችል የአጻጻፍ ዘዴ መሸጋገር አለብን። ለዚህ የሚሆን የመጀመሪያውን ስራ ዳቪቶ መስፈን እየሰራ ነው። በእኔ ዕምነት እስካሁን ድረስ ከኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እሱ ብቻ ነው ዕውነተኛውን የሳይንስ ቁልፍ ማግኘት የቻለው። ይህ የሱ አዲስ ሳይንሳዊ ጥናት በፍልስፍና ቢደገፍ የበለጠ ጥራትን ሊያገኝ ይችላል ብዬ እገምታለሁ። የሳይንስን መነሻ ለመረዳት ይበልጥ ይረዳናል። ሌሎችም ምሁሮች የሱን ፈለግ መከተል አለባቸው። ሁሉም እንደየአቅሙ በየሙያው እንደዚህ ዐይነት ሳይንሳዊ ጥናት ቢያበረክት የህብረተሰባችንን ችግር ለመረዳትና መፍትሄ ለመስጠት ትልቅ ስራ ሰራን ማለት ነው። ሁላችንም መረዳት ያለብን አንድ ጉዳይ አለ። የምዕራቡ ዓለም ህብረተሰብ የሰው ልጅ የመጨረሻው ታሪክ አይደለም። ወይም ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በራሳቸው ብቻ በቂ አይደሉም። የአንድ ህብረተሰብ ዕድገት በሊትሬቸር፣ በግጥምና በድራማ፣ በውብ አርክቴክቶችና ዕቅድ ባላቸው የከተማ አገነባብ፣ በዕደ-ጥበብ ስራና አካባቢን በመንከባከብና በሌሎች የሰውን አስተሳሰብ ረጋ የሚያደርጉና እንደሰውም መሆኑን በሚያስገነዝቡት ልዩ ልዩ ስራዎች የሚገለጽ ነው። ስለዚህም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ህብረተሰብአዊ ችግሮች ያሏቸው አገሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈውን የተወሳሰበ ችግርና እንዲሁም ዕድገትን ጎታች አስተሳሰብ፣ ከዚያም በላይ በተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተዘበራረቀውን ሁኔታ ለመቅረፍ የሚቻለው በነጻ ገበያ ፖሊሲ አማካይነት ሳይሆን በባህል ሬናሳንስ አማካይነት ብቻ ነው። ይህም ማለት በአንድ ጊዜና በተከታታይ ሁለ-ገብ የሆነ የባህል አብዮት ማካሄድ ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ብቻ ነው አንድ ህብረተሰብ ሊተሳሰርና መንፈሳዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው። ለዚህ ዐይነቱ ዕድገት አሁንም ሃሳብና(Idea) የመንፈስ ጥንካሬ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ። አንድ ህዝብ በሃሳብና በመንፈስ ጥንካሬ ብቻ ነው ራሱን ሊለውጥና ውብ ውብ ስራዎችን ሊሰራ የሚችለው። መልካም ግንዛቤ!

Links

FORUM – Inforadio
Drama oder Chance –
Folgen des Ukraine-Kriegs für Afrika


(Bild: rbb/Matthias Schirmer)

Beitrag: Audiodatei

Weitere Links:

Books

African Predicaments & the Method of solving them effectively

 

(English) Book – 30. August 2016


 

Deutsch – Amharisch / Amharisch – Deutsch

von Fekadu Bekele und Bosena Negussie | 25. Januar 2019

 

 

Capitalism

Fekadu Bekele

 


Fekadu Bekele

Gesellschaftsformation und Artikulation von Produktionsweisen in Äthiopien