[gtranslate]

ፓለቲካም እንደሳይንስና ሂሳብ መታየት ያለበት ጉዳይ ወይስ ሳይንሰ-አልባ! ክፍል ሁለት

                                                                       ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

      መግቢያ                                                                                                                                                                                                                                                                        ነሐሴ 29፣ 2019

በፈረንጆች አቆጣጠር በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም ይህንን አርዕስት በሚመለከት ሰፋ ያለ ሀተታ እንደሰጠሁ ይታወቃል። በዚያ ጽሁፌ ላይ ለማመልከት እንደሞከርኩት ፖለቲካ የግዴታ ሳይንሳዊ በሆነ መልክ መታየት እንዳለበትና ከፍተኛ ግንዛቤን ወይም ደግሞ ጭንቅላትን ማስጨነቅ እንደሚያስፈልግ ነው።  በዚያን ጊዜና በየጊዜው የምጽፋቸው ጽሁፎች የቱን ያህል ግንዛቤ ውስጥ ይግቡ አይግቡ አላውቅም።

አብዛኛዎቻችን የአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ሁኔታ አስመልክተን ለአንባቢያን ሀተታዎች በምናቀርብበት ጊዜ ለማለት የምንፈልገው ነገር እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ይሁንና ግን ለማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት ወይም ሀተታ የቱን ያህል ተጨባጩን የአገራችንን ሁኔታና፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና እንዲሁም በስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎችን የህሊና አወቃቀር ያንፀባርቅ አያንፀባርቅ መገመት የሚቻለው እያንዳንዱ ግለሰብ የሚከተለውን የአፃፃፍ ስልት በሚገባ የተረዳን እንደሆንና፣ እኛም አንባቢዎች ስለሳይንሱ ግንዛቤ ያለን ከሆነ ብቻ ነው። እንደሚታወቀው በሳይንስ ዓለም ውስጥ አንድን በምድር የሚታይ ተጨባጭ ሁኔታና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ መመርመሪያ ዘዴ ስላለ ይህንን ለያይተን ማወቅ እስካልቻልን ድረስ ማንኛውም በጥሩ እንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ የሚጻፉና የምናነባቸው ጽሁፎች ዕውነት ሊመስሉን ይችላሉ። በጽሁፍ ላይ የሚቀርቡ ሀተታዎች በዐይናችን እንደምናያቸውና በእጃን እንደምንዳስሳቸው ዕቃዎች ስላይደሉና፣ የአንድን አገር ተጨባጭ ሁኔታና የታሪክ ሂደት ለማሳየት ተብለው ስለሚቀርቡ የማሳሳት ኃይላቸውም ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።  ስለሆነም የያንዳንዳችን የጽሁፍ ስልት  ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴን ይከተል አይከተል መገመት የሚችለው  በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን አንድ ጸሀፊ በተለይም የህብረተሰብን ችግር ወይም ጥያቄ አንስቶ አንድ ጽሁፍ ለአንባቢያን ሲያቀርብ አንድ የሚመራበት የአሰራር ስልትና ሳይንሳዊ ዘዴ እንዲሁም ፍልስፍናዊ መሰረት መኖር አለበት። እንዲያው ለመጻፍ ብቻ ተብሎ የሚጻፍና ለአንባቢያን የሚቀርብ ሀተታ በተለይም የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት ለመቅረጽ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውዥንብር ውስጥ ይከተዋል። የህብርተሰቡንም ችግር በቅጡ ስለማይረዳ መፍትሄም ለመፈለግና ተግባራዊ ለማድረግ ግራ ይጋባል።

ከዚህ ስንነሳ ባለፉት 26 ዓመታት በተለያዩ ድህረ-ገጾችም ሆነ መጽሄቶች ላይ ለአንባቢያን የቀረቡትን ጽሁፎች ወይም ሀተታዎች ጠጋ ብሎ ለተመለከተ እጅግ አወዛጋቢ ሁኔታዎች ውስጥ የከተቱና ከሳይንስና ከፍልስፍና አንጻር ለመገመት ወይም ለመመዘን የሚያስቸግሩ ለመሆናቸው የሚያጠራጥር አይደለም። በአገራችን ታሪክ ውስጥ በተለይም የህብረተሰብ ታሪክን(Social History) ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር የመመርመር ልምዱ ስለሌለና፣ የሚጻፉትም ጽሁፎች „ከታሪክ አንፃር“ ብቻ በመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ ህዝባችን የተጓዘበትን የውጣ ውረድ ጉዞ፣ ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ግኑኝነትና፣ እርስ በርሱም ያደርግ የነበረውን በተለያየ መልክ የሚገለጸውን ግኑኝነት ለመረዳት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቀናል።  በመሆኑም በተለያየ የታሪክ ወቅት ከልምድ አንፃር  የዳበረውን የማሰብ ኃይል ወይም ደግሞ እንደባህል በሚወሰድ ልማዳዊ አሰራር የተነሳ ሊዳብር ያልቻለውን የማሰብ ኃይልና ለዕድገት ወይም ለስልጣኔ እንቅፋት የሆነውን የአሰራር ስልት  ከሳይንስ አንፃር ከመመርመር ይልቅ በስሜት ብቻ በመመራት ለመተርጎም በመብቃታችን ህዝባችንን ነፃ ለማውጣት እያልን የምናካሂደው የፖለቲካ ትግል ከጥራት ይልቅ ወደ ንትርክ እንድናመራ አድርጎናል። ህዝባችን ርስ በርሱ እንዲጠራጥር ከማድረጋችን አልፈን ኑሮው ሁሉ የባሰውን እንዲመሰቃቀልበት ለማድረግ በቅተናል። ለምን እንደሚኖር? ለምን እንደተፈጠረ? ምን ምን ነገሮችን መስራት እንዳለበት? የኑሮስ ትርጉሙ ምን እንደሆነና ወዴትስ እንደሚያመራ? እንዳያውቅ አድርገነዋል።

በአውሮፓው የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ከግሪኩ ስልጣኔ ጀምሮ እስከ አውሮፓው የመጨረሻው ማዕከለ-ዘመን ድረስና ካፒታሊዝም እንደህብረተሰብ ስርዓት የበላይነትን መቆጣጠር እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ እንደሳይንሳዊ መመሪያዎች የተወሰዱ የግንዛቤ፣ የአሰራርና የአጻጻፍ ስልቶች አሉ።  በየኢፖኩ ብቅ ብቅ ያሉ ምሁራን የየህብረተሰቦቻቸውን ፖለቲካዊ አወቃቀርና የባህል ሁኔታ ለመረዳትና ለመግለጽ የሚችሉብት ዘዴዎች ነበሯቸው። አሁንም አሏቸው።  ዝም ብለው በአቦሰጡኙ የሚጽፉና በጭፍን የሚሸመጥጡ ሳይሆኑ ረጋ ባለመልክና በተቀነባበረ መልክ የሚጽፉ በመሆናቸው በየጊዜው የነበረውን የየአገሮቻቸውን ችግሮች ለመረዳት ይህን ያህል አስቸጋሪ አልነበረም። በአጭሩ አጻጻፋቸው ሳይንሳዊውን ዘዴ የተከተለ ነው ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ቀደም ብዬ በተለያዩ ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሁሉም ምሁሮች፣ ወይንም ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች በጊዜው የነበረውን የህብረተሰብ ችግር ለመረዳት የሚመሩበት ዘዴ አንድ ወጥ አልነበረም። ይሁንና አንድ የሚስማሙባቸው ሃሳቦች ነበሩ። ይኸውም ከጊዜው ከነበረው ዕድገትን አፋኝ ስርዓት የግዴታ መላቀቅ በሚለውና፣ ህብረተሰቡን ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል በሚለው ላይ ነበር። ወደእኛ አገር ስንመጣ ግን ሁሉም ነገር የተምታታብን ይመስላል። ለምን ዐይነት ስርዓትና በምን ፍልስፍናና ሳይንስ ላይ ተመርኩዘን እንደምንታገል ግልጽ አይደለም። ስለሆነም በተለይም ለታዳጊው ትውልድ እስካሁን ያስተላለፈነው መመሪያ የምንለው የአሰራርና የመመርመሪያ ዘዴ የለንም። በአጭሩ ሁላችንም በስሜት የምንመራ እንጂ የመመራመሪያ ሳይንሳችንና ፍልስፍናችን ይህ ነው፣ ስለዚህም እሱን መሰረት አድርገን ነው የችግሩን ዋና ምክንያት መረዳት የምንችለው ብለን የተጠጋጋ መፍትሄ ለመፈለግ ስንታገል አይታይም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ቢያንስ ከአርባ ዓመታት በላይ ጊዜ ማባከናችን ብቻ ሳይሆን፣ ህብረተሰብአችን ሊወጣው የማይችለው ማጥ ውስጥ በመክተት ፍዳውን እንዲያይ ለማድረግ በቅተናል። በዚህ ዐይነቱ እጅና እግር የሌለው አሰራር እስከመቼ ድረስ እንደምንጓዝ  አይታወቅም። እንደምከታተለው ከሆነም መፍትሄ የሚገኝለት አይመስለኝም። በሌላ ወገን ግን ተስፋ መቁረጥ የለብንም። የመጨረሻ መጨረሻ የሚሞተው ተስፋ ብቻ ስለሆነ፣ እስከዚያ ድረስ መፍጨርጭሩ ክፋት ያለው አይመስለኝም።

         የፓለቲካ ትግል ሲካሄድ አብዛኛውን ጊዜ ግንዛቤ ውስጥ የማይገቡ ጉዳዮች !!

በአገራችን ታሪክ ውስጥ ለስልጣንና ለዲሞክራሲያዊ ነፃነት የሚደረገው ትግል አብዛኛውን ጊዜ  ከአመጽ ወይም ከጦር ትግል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ትግሉ በአንዳች ፍልስፍና ላይ እንዳይመሰረትና ሳይንሳዊ መመሪያ እንዳይኖረው ለመሆን በቅቷል።  ስለሆነም ይህንን የትግል ስልት ይዘው የሚታገሉ ኃይሎች እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄረሰብም ሆነ የህብረተሰብ ክፍል፣  ሁለንታዊ ፍላጎቱን በማጥናትና ስልጣን ስንይዝ በዚህ መልክ ነው  ልናሟላ የምንችለው በማለት ሳይሆን ትግላቸውን የሚያካሂዱት እንዲያው በስሜት ብቻ በመነዳት ነው። ስለሆነም አንድ ሰው እንደሰው አይታያቸውም። ይህም ማለት በተለያየ መልክ የሚገልጽ ፍላጎት እንዳለውና እነዚህን ፍላጎቶቹን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ሊያደርግባቸው የሚያስችሉት መሳሪያዎች ወደ ተግባር መመንዘር እንዳለባቸውና፣ ይህንንም ለማድረግ የግዴታ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መመሪያዎች መኖር እንዳለበቻው ግንዛቤ ውስጥ አይገቡም። ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ ይወለድ ማንኛውም ሰው ወይም ግለሰብ  ሰው እንደመሆኑ መጠን የተከማቸ የማሰብ ኃይል አለው። የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም እንደ የሁኔታው ቁሳቁሳዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ይፍጨረጨራል። ግለሰብአዊ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰብአዊ አካልም እንደመሆኑ መጠን ቤተሰብ በመመስረትና ከሌላው ተመሳሳዩ ጋር ግኑኝነት በመፍጠር የማሰብ ኃይሉን ማዳበሩ ብቻ ሳይሆን በሚኖርበት አካባቢ ታሪክን ለመስራት የሚያስችሉትን ነገሮች ቀስ በቀስ ተግባራዊ ያደርጋል። ይህንን ማድረግ የሚችለው በጦርነት ካልተጠመደ፣ ወይም ጭንቅላቱ አንድ ባህል በሚመስል፣ ይሁንና ዕድገትን በሚቀናቀን ነገር ካልተጠመደ በስተቀር ነው። በተለይም በአካባቢው ከሱ የተሻለ የሚያስብ የህብረተስብ ኃይል ካለ በሱ አማካይነት ጭንቅላቱን በማሾልና አዕምሮውን በማደስ ልዩ ልዩ ነገሮችን ይፈጥራል። በስራ ክፍፍል ውስጥ በመሰማራት ልዩ ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሆን  የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው ?  አብዛኛውን ጊዜ ለፖለቲካ ስልጣን እንታገላለን ብለው እዚህና እዚያ የሚፍጨረጨሩ፣ ወይም በጦር ትግል አማካይነት ስልጣንን ለመቀዳጀት የሚፈልጉ ኃይሎች ትግል ብለው ሲጀምሩ ከመጀመሪያውኑ የማያስቧቸው መዓት ነገሮች አሉ። ራሳቸው ሰው መሆናቸውንና አለመሆናቸውን በፍጹም አይጠይቁም። በተለያየ መልክ የሚገለጸውንም ፍላጎታቸውን ከዚህም ከዚያም በማግኘት በስሜት ብቻ ስለሚጠቀሙ፣ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉ ልዩ ልዩ ነገሮችን ለመስራትና መልክ ለመስጠት ምን ያህል ጊዜና ዕውቀት እንደፈሰሰበትና፣ ቁሳቁሶቹን ሰርተው የሚያቀርቡ ሰዎች ከፍተኛ እንክብካቤና ክብር እንደሚያስፈልጋቸው በፍጹም አይረዱም። ብቻ ሁሉም ነገር ብዙ ሳይታስብበትና ሳይለፋበት ተሰርቶ የሚቀርብ ስለሚመስላቸው ያንን በመጠቀምና ራሳቸውን በማደለብ አካባቢያቸውን ማመስ ይጀምራሉ። እንደሰው ይንቀሳቀሱ እንጂ የማሰብ ኃይል እንዳለው እያንዳንዷን የሚያደርጓትን ድርጊትና ሊያስከትል የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታ ማገናዘብ ስለማይችሉ ሳያውቁት ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ቀውስ  እንዲፈጠር ዋና ምክንያት ይሆናሉ። አንድ ግለሰብ በአምላክ የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን የራሱ ውስጣዊ ኃይል እንዳለውና፣ ነፃነትን እንደሚፈልግና፣ ነፃነትን እስከተቀዳጀ  ጊዜ ድረስ ብቻ የመንፈስ ደስታን በመቀዳጀት የማሰብ ኃይሉ ከፍ እንደሚልና አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር እንደሚችል በፍጹም ስለማይገነዘቡ ህብረተሰብአዊ ዕድገትን ያሰናክላሉ። ስለሆነም አንድ ግለሰብም ሆነ በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ ታሪክን እንዳይሰራ፣ ርስ በርሱ በመገናኘት ወደ ህብረተሰብአዊ ኃይል እንዳይሸጋገር የሆነውን የማይሆነውን ነገር በማውራትና ጭንቅላቱ በአልባሌ ነገሮች እንዲጠመድ በማድረግ በሚኖርበት አካባቢ ራሱን እንዳይገልጽ ያደርጉታል። በራሱ ላይ ዕምነት እንዳይኖረው በማድረግ ህይወቱን በሙሉ ያጨልሙበታል። እንደዚህ ዐይነት ህዝብ ደግሞ የህይወትን ትርጉም ስለማይረዳና፣ ህይወት ማለት ምን ማለት ነው? ለምንድ ነው በዚህች ዓለም ላይ የምኖረው? ዓላማዬስ ምድነው?  ወዴትስ ነው የምጓዘው? ብሎ ለመጠየቅ ስለማይችል፣ መሪ ነን በሚሉት ወይንም በገዢ መደቦች እንደከብት እየተነዳ ፍዳውን እያየ እንዲኖር ይገደዳል። ባጭሩ የድሀነት፣ የረሃብና የበሽታ ሰለባ ለመኖን ይበቃል። ሙሉ በሙሉ ነፃነቱን በመግፈፍ የኑሮን ትርጉም ሳይረዳ ወደ ማይቀረው ዓለም ይሰናበታል።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ትግል ብለው የጀመሩ፣  ወይንም ስልጣን ላይ ሆነው ታሪክን መስራት ያልቻሉ የአገራችን አገዛዞች በአጠቃላይ ሲታይ ስለሰው ልጅና ከዚያም በላይ ስለህብረተሰብ የነበራቸው ግንዛቤ ዜሮ ነው ማለት ይቻላል። ለብዙ አስርት ዐመታት ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያሉት በጊዜው ህዝባችንን እንደሰው ባለመቁጠራቸውና፣ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መመሪያም ስላልነበራቸው ህዝባችን እንዴት አድርጎ ደረጃ በደረጃ ጤናማ ህብረተሰብ መመስረት እንዳለበት የሚያስችሉትን መሰረታዊ ነገሮች ሊያነጥፉ ወይም ሊያዘጋጁ በፍጹም አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ህብረተሰብአዊ ክፍተት እንዲከሰት በማድረግ ለሌላ ቀውስ ዳርገውን ጥለው ማለፍ ችለዋል። በእነሱ ዕምነት፣ ዕምነት እንበለውና ህዝባችን እንደሰው የሚታይ አልነበረም። ስለሆነም በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ ፍላጎት እንዳለውና እነዚህም ደግሞ ከሳይንስ አንፃር እየተጠኑ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ በመሆን ህዝባችን እንዲተሳሰር ለማደረግ አልቻሉም። በራሳቸው ዓለምም የሚኖሩ ስለነበሩ ወይ ለዘለዓለም ስልጣን ላይ የሚቆዩ የሚምስላቸው ስለነበሩ፤  ካሊያም ደግሞ „እኔ ከሞቱኩ በኋላ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው“ አህያ የሚቀጥለውና ተከታታዩ ትውልድ ዕጣ ምን ሊሆን ይችላል ? ብለው ለመጠየቅና ለማሰብ ባለመቻላቸው በግትር ሃሳብቸውና በጭፍን አስተሳሰባቸው በመግፋት የህዝባችንን ኑሮ በማጨለምና የአገራችንን ዕድል በማጣመም ወደ ማይቀረው ዓለም ለማለፍ በቅተዋል።

ለፖለቲካ ስልጣን እንታገላለን ብለው እዚህና እዚያ የሚራወጡትንና ብሄረሰብአችንን  ነፃ እናወጣለን ብለው  የጦር ትግል የሚባለውን ፈሊጥ የጀመሩትንንም ሁኔታ ስንመለከት ከላይኛዎቹ ስልጣንን ጨብጠው ከነበሩ አገዛዞች የተሻሉ አልነበሩም፤ አይደሉምም። በመጀመሪያ ደረጃ ከአንዳዶቹ በስተቀር የአብዛዎቹ ፍልስፍና ወይም የትግል መመሪያ ምን እንደሆነ በፍጹም አይታወቅም። ስለሆነም እንወክልዋለን የሚሉትን ህዝብ ፈላጎት ምን ምን እንደሆነ በቅጥ የተገነዘቡ አልነበሩም። ስለሆነም ትግል ብለው ሲጀምሩ የመጨረሻ መጨረሻ ዓላማቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም። ፖለቲካ የሚባለውን ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ከፍልስፍናና ከተፈጥሮ ሳይንስ ለይተው ያዩ ስለነበርና ስለሚያዩም  ስልጣን ላይ ቢወጡ እንኳ በመጀመሪያ ደረጃ ምን ምን እርምጃዎችን መወሰድ እንዳለባቸውና፣ ህብረተሰብም እንዴት ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ መገንባት እንዳለበት ግልጽ የሆነ አመለካከት አልነበራቸውም፤ የላቸውምም። ስለሆነም በእልክ የጀመሩት ትግል ወዴት እንደሚያመራ ባለመገንዘባቸውና መመሪያቸውም ምን መሆን እንደነበረበት ማጤን ባለመቻላቸው ከዛሬው ሁኔታ ስንነሳ የመቶ ሚሊዮን ህዝብ ዕድል እንዲጭልም፣ ዘለዓለሙን ፍዳውን እያየ እንዲኖር ለማድረግ በቅተዋል። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ቢያስቡበትና ራሳቸውንም ያወቁ ቢሆን ኖሮ የሚፈጥሯቸው ወይም የሚጽፏቸው አዳዲስ ነገሮች አልነበሩም። ሁሉም ተዘጋጅተው ያሉ ስለሆነ እነሱን ፈልጎ ማግኘትና መመሪያ በማድረግ አዲስና አሳቢ ህብረተሰብ ለመመስረት ይችሉ ነበር። በሌላ ወግን ግን ገት ስላልነበራቸውና የአስተሳሰብ አድማሳቸውም ውስን በመሆኑ ጠቅላላውን ህዝብ የሚያስተሳስርና የሚያስተባብር ፖለቲካዊ ፕሮጀክት ለመንደፍ በፍጹም አልቻሉም። የአንድ አገር እህትማማችና ወንድማማች ህዝብ ርስ በርሱ እንዲጠላላ ለማድረግ በቁ።  ለብዙ መቶ ሺህ ህዝብ ማለቅ፣ መሰደድና መንገላታት ምክንያት ሆኑ። ይህን ሁሉ አድርገውም ዛሬም ቢሆን ፀፀት የሚሰማቸው  አይደሉም። ወንድማማች ህዝብ ርስ በርሱ እንዲጨራረስ ካደረጉ በኋላ፣ አገር እንዲፈራርስ ሁሉን ነገር ካዘጋጁ በኋላ፣ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነት እንዲፈጠር ካደረጉ በኋላ፣ ወጣቱ ትውልድ ጭንቅላቱ ቦዝኖ የሚያደርገውን ሁሉ እንዳያውቅ ካደረጉ በኋላ፣… ወዘተ…. ወዘተ. ዛሬም ቢሆን የሰራነው ሁሉ ትክክል ነበር ይሉናል። „ይህ ትውልድ ከኛ የሚማረው ብዙ ነገር አለ“ እያሉ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ነገር ይነግሩናል። ማሰብና ጥያቄ ለማቅረብ እንደማይችል ሰው ሁሉ  የሆነውን ያልሆነውን በመናገር ወደ ሌላ ስህተት ውስጥ እንድንገባ ያደርጉናል። እነዚህ ሰዎች ወይም ድርጅት አለን የሚሉ ዛሬም የምንታገለው እንደወትሮው ስለሆነና ያላጠናቀቅነው ፕሮጀክት ስላለ ዝም ብላችሁ አዳምጡን ይሉናል።

የዚህ ሁሉ ችግር አሁንም ቢሆን የመንፈስን የበላይነት አለማስቀደምና በጉልበት በመመካት ብቻ የበላይነትን ለመቀዳጀት ከማሰብ የመነጨ ግትር አስተሳሰብ ነው። አንድ ሰውና ህብረተሰብ ምን ማለት እንደሆኑና፣ አንድ አገር ታሪክ የሚሰራበት መድረክ መሆኑን ተገንዝቦ መወሰድ ያለባቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ለመሆን አለመፈለግና፣ እኔ የምለው ነገር ብቻ ነው ትክክል በማለት የሚካሄድ አብዛኛውን ጊዜ በስሜት ላይ የተመረኮዘ የትግል ስልት ነው። አገር፣ ህዝብ፣ ህብረተሰብ፣ ግለሰብአዊ ነፃነትና ህብረ-ብሄር የሚባሉት ፅንሰ-ሃሳቦች አንድ ላይ የተያያዙ መሆናቸውን ባለመረዳት ሁሉም በመሰለው መልክ ይታገላል። የብዙዎቻችን ልምድ ከተወሰነ ነገር ስለማያልፍና ህብረ-ብሄርና ህብረተሰብ የሚባሉትን መሰረታዊ ነገሮች ከጭንቅላታችን ጋር ለማዋሃድ ባለመቻላችንና ትርጉማቸውንም በሚገባ ለመረዳት ስለማንፈልግ ሁልጊዜ በራሳችን ዙሪያ ብቻ እንሽከረከራለን። ችግሩ የት ላይ ነው ? ብለን ለመጠየቅ ስለማንቃጣ ከአንድ ስህተት ወደ ሌላ በመሸጋገር እኛ ግራ ተጋብተን ወጣቱንም ትውልድ ግራ እናጋባለን። ይህ ዐይነቱ አደገኛ አስተሳሰብና በአንዳች ፍልፍስፍና አለመመራት የኛ ችግር ብቻ ባለመሆኑ በየአገሮች የተቀመጡ አገዛዞችና ተቃዋሚ ነን የሚሉ ኃይሎች ግራ በመጋባት ህዝቦቻቸውን እያተራመሱ ነው። በየአገሩ ያለውን የሰውና የተፈጥሮ ሀብት በስነስርዓት ለመጠቀም ባለመቻላቸው በተለይም ወጣቱ ትውልድ ባህርን እያቆራረጠ፣ ከሞት የሚተርፈው ደግሞ ወደ አውሮፖና ወደሌሎች አገሮች በመምጣት አዲስ ህይወት ለመምራት እንዲፍጨረጨር ተገዷል።

ፖለቲካ አገር መገንቢያና ታሪክ መስሪያ መሳሪያ መሆኑን ያለመረዳት ጉዳይ !

ዛሬ በአገራችንና በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች የሚታየው የፖለቲካ ውዝግብ፣ የመንግስትን መኪና ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የአገርን ሀብት መዝረፍና ማውደም፣ እንዲያም ሲል ወደ ውጭ አገር እያሸሹ የካፒታሊስት አገሮችን ሀብት የባስውን ማደለብ፣ በዚያው መጠንም ወደ ውስጥ ኋላ-ቀርነትንና ድህነትን ማስፋፋትና ህዝብን አቅመ-ቢስ ማድረግ የፖለቲካ ትርጉምን ካለመረዳት የመነጨ ነው።  ይህ ከላይ በክስተት ደረጃ የምናየው እንደ ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ቢሆንም፣ ዋናው ምክንያት ግን ስልጣንን የጨበጡ የገዢ መደቦችም ሆነ የተቀረው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኢሊት ብሄራዊ ስሜትነትን ሊያዳብር የሚያስችለው ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና ባለመኖሩ ነው። ሰብአዊነትን የሚያላብስ፣ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በመረዳት ታሪክን ሊያሰራ የሚያስችል ንቃተ-ህሊና ለማዳበርና ጭንቅላቱ ውስጥ ለማዋሃድ ባለመቻሉ ኤሊት ነኝ የሚለው አገሩን እያፈራረሰና የራሱን ህዝብ አቅመ-ቢስ አድርጎታል ። በተጨማሪም ዘመናዊ ትምህርት የሚባለው የኢሊቱን ጭንቅላት ከማደስና ብሄራዊ ኃላፊነትና ስሜት እንዲሰማው ከማድረግ ይልቅ በማጨለሙ የሚሰራውን ነገር እንዳይገነዝብ አግዶታል። በዚህም ምክንያት የተነሳ  በተበላሸ ትምህርት የስለጠነው ኤሊት የኢምፔሪያሊስቶች አሽከር በመሆን ከውስጥ ሀብት እንዲዘረፍ በማድረግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በየአገሩ ያለ ሰፊ ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ በቃ። እያንዳንዱ ግለሰብ በአምላክ ምስል የተፈጠረ መሆኑን በመገንዘብ ተፈጥሮ የሰጠችውን ጸጋ የባሰውኑ ቆንጆ ከማድረግ ይልቅ እንዲያበላሻትና አካባቢውን እንዲያዝረከርክ ተገደደ። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቱ የሰው ጉልበት ዋናው የሀብት ፈጠራ መሰረት ነው የሚለውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግ በደንብ  ለመረዳት ባለመቻሉ በየአገሩ ያለ ህዝብ በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ጥሬ-ሀብቶችን እያወጣ ወደ ተጨባጭ ሀብት እንዲለውጣቸውና ኑሮውን እንዲያሻሽል አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር አልቻለም። በተለይም በሳይንስ ያልተፈተነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የሰው ልጅ ጉልበትና የጥሬ-ሀብት እንዲባክኑ ተደረጉ።

በተለያዩ ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከእነ ፕላቶና እስከ ሄግል እንዲሁም ካንት ድረስ የነበሩት የአውሮፓ ምሁራን የንቃተ-ህሊና መዳበር በህብረተሰብአዊ ግንባታ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በእኩልነት ላይና እንዲሁም በሌሎች የአንድን ህዝብ የሚመለከቱ ማቴርያላዊና የህሊና ነገሮች ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ለማሳየትና ለማስተማር እንደቻሉ ነው። በእነዚህ ታላላቅ ምሁራን ብቻ ሳይሆን በእነ አውግስተስ ኮምቴና ቪኮ ምርምር መሰረት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ቀስ በቀስ ከማቴሪያላዊ ዕድገት ጋር በመጣመር ሊያድግ እንደሚችል ነው የሚያረጋግጡት። በመጀመሪያ ደረጃ የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚታዩትን ተፈጥሮአዊ ከሆኑ ነገሮች በስተቀር ማንኛውንም ቁሳቁሳዊ የሆኑ ነገሮችን የመፍጠር ኃይል አለው። እንደ ቋንቋና ፊደላትንም የመሳሰሉትን በመፍጠር ርስ በርሱ በመግባባትና በረቀቀ መልክ በማሰብ ከአንድ የዕድገት ደራጃ ወደ ሌላ ለመሸጋገር እንደሚችል ነው። በሌላ ወገን ሳያውቀው ወይም ሳያስብ ልማዳዊ የሚባሉ ነገሮችን በመፍጠር የማሰብ ኃይሉ እንዲቆለፍ በማድረግ በዕድገቱ ሊገፋበት አይችልም። ከዚህም በላይ ሀብትን የሚቆጣጠር የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ሲልና ሲደላደል ህብረተሰቡን አንቆ ለመያዝና ለመዝበዝ የሚያስችለው ርዕዮተ-ዓለም በመፍጠር አንድ ህዝብ በዕድገቱ እንዳይገፋበት ያደርጋል። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፀር በመሆን ህዝብ በጦርነት እንዲታመስ ያደርጋል። ይህ ዐይነቱ ፀረ-ዕድገት ሂደት ሊገታ የሚችለው በአውሮፓ ምድር ውስጥ እንደታየው በከፍተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴና የህብረተሰብ ኃይል ንቃተ-ህሊና መዳበር ብቻ ነው። በዚህ አማካይነት የስራ ክፍፍል ሲዳብርና ከተማዎች ሲገነቡ አንድ ህብረተሰብ መተሳሰሩ ብቻ ሳይሆን  ህብረተሰቡን ሊመራና አቅጣጫ ሊሰጠው የሚችል የህብረተሰብ ኃይልም ይፈጠራል። እዚህና እዚያ የዕደ-ጥበብ ሙያዎች ሲስፋፉና ኢንዱስትሪዎች ሲተከሉ በኢኮኖሚ የበላይነትን የተቀዳጀው ኃይል ብሄራዊ ባህርይ ያዳብራል።  ስለሆነም  የበላይነቱን ላለማጣትና ከውጭ የሚመጣበትን ግፊት ለመቋቋም ሲል የግዴታ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔውን በተወሰነ ክልል ብቻ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ እንዲስፋፉ ያደርጋል። በዚህ ዐይነት ብሄራዊ እኮኖሚ ሲዳብር ህብረተሰቡ፣ በተለያዩ በግልጽ በሚታዩና በማይታዩ ነገሮች በመተሳሰር የዚያ አገር ሙሉ ዜጋ መሆኑን ያረግጋጣል። ይህ ዐይነቱ የዕድገት ሂደት ለፖለቲካ ብስለትም መንገዱን ክፍት ስለሚያደርግ እዚህና እዚያ የየራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ ይሁንና ደግሞ ብሄራዊ ነፃነትንና ዕድገትን የማይቀናቀኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በመፈጠር የፖለቲካ መድረኩን ያሰፉታል።

በአውሮፓ ምድር ውስጥ በፖለቲካው መስክ የተካሄደው ትግል በየኢፖኩ የሚለያይና ብዙ ውጣ ውረድን አሳልፎ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው። ቀድሞም ሆነ ዛሬ ልክ አገራችን ውስጥ እንደምናየው ኃላፊነት የጎደለው ፓለቲካዊ አካሄድና የርስ በርስ ግብግብ በአውሮፓ ምድር ውስጥም ነበር። አንዳንዶቻችን እንደምንገምተው አውሮፓውያን እንደ አምላክ ሆነው ከዕውቀት ጋር የተፈጠሩና ካለምንም ችግር ከተማዎችን በመገንባትና ሁሉንም ነገር በማደራጀትና በመፍጠር እዚህ ቦታ የደረሱ ሳይሆኑ በመሀከላቸው ብዙ ንትርክንና ትግልን ካሳለፉ በኋላ ነው። እስከ 13ኛ ክፍለ-ዘመን ድረስ የአውሮፓ ህዝብ ፍዳውን ያይና በበሽታና በድህነት የሚሰቃይ ነበር። የፊዩዳል መሪዎችና ቀሳውስቶች የሚሰሩትን ነገር የሚያውቁ ስላልነበር ህዝብን ለድህነት፣ ለጦርነትና ለበሽታ ይዳርጉት ነበር። ይህ ሁኔታ ሊገታ የቻለው የተገለጸላቸው ምሁራን ጣልቃ መግባት ከጀመሩ በኋላና፣ በተለይም ደግሞ የህብረ-ብሄር(Nation-State) ምንነትና ትርጉም ግንዛቤ ውስጥ ከተገባ በኋላ ነው። ይህ ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ የበለጠ መልክ ለማስያዝ ሲባል በተለይም በሁሉም አቅጣጫ አገርን የመገንባት አስፈላጊነት ግልጽ እየሆነ ይመጣል። በተለይም በመርከንታሊዝም(Mercantlism) አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአዳዲስና ለነቁ ኃይሎች መንገዱን ያመቻቻል። በሌላ ወገን ግን የሞናርኪ አገዛዞች ሳያውቁት የሚቀናቀኗቸውን ኃይሎች  እንደ አሸን እንዲፈልቁ ያደርጋሉ። በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቲዎሪ ሲዳብርና ሲስፋፋ የሞናርኪዎች አገዛዝ ዘመን እያከተመ መምጣት ይጀምራል።  ከዚያ በኋላ ነው የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ ወይም የረቀቀ እጅ አስፈላጊነት መሰበክ የተጀመረው። በሌላ አነጋገር እነ አዳም ስሚዝ እንደሚያስተምሩት ሳይሆን የአውሮፓው ኢኮኖሚ ማደግና መልክ መያዝ የጀመረው በተገለጸላቸው የፍጹም ሞናርክዎች አገዛዝ አማካይነት ነው። የካናል ሲሰተምና ትላልቅ ቤተ መንግስታት ለመሰረታና ለመገንባት የቻሉት በግለሰቦች ተነሳሽነት ሳይሆን በተቀነባበረ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው። የኋላ ኋላ ግን በሩቅ ንግድ የናጠጡ ሀብታም ነጋዴዎች በከተማ ግንባታ ውስጥ በመሳተፍ ለካፒታሊዝም ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማድረግ ችለዋል። ግለሰብአዊ  ፈጠራና ድርጊት ተግባራዊ መሆን የጀመሩት ሁኔታዎች እየተመቻቹ ከመጡ በኋላ ነው ማለት ነው። ይህ ሁሉ በመጣመርና ህብረተሰቡ መፍታታት ሲጀምርና ከተተበተበበት ሰንሰለት ሲላቀቅ ራሱን ማግኘትና ፈጣሪ መሆን ይጀምራል። ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና የምሁራዊ ኃይል መዳብርና የከበርቴው መደብ ብቅ ማለትና ህብረተሰብአዊ ኃይል መሆን የፖለቲካ ተወዳዳሪ አድርጎታል። የራሱን ፍላጎት ተግባራዊ ማድረግ የሚችል መሆኑን ሲረዳ በሞናርኪ አገዛዞች ላይ ጫና ማድረግ ይጀምራል። በተለይም በጀርመን አገር የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ብቅ ማለትና ብዙ ተከታዮችን ማፍራት በመቻሉና፣ ወደ ሌሎች አገሮችም በመስፋፋቱ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የፖለቲካ ማትሪክሱን መቀየር ተችሏል። የካቶሊክ ሃይማኖትም የነበረውን የበላይነት ሲነጠቅ አዳዲስ ተወዳዳሪ ሃሳቦች ብቅ በማለት ለሳይንስና ለፍልስፍና አመቺ ሁኔታዎች መፈጠር ቻሉ። በኋላ ደግሞ በእንግሊዝ አገር የፕርቴስታንት ሃይማኖት በካቶሊክ ሃይማኖት ላይ የበላይነትን ሲቀዳጅ የፖለቲካ ማትሪክሱ መቀየሩ ብቻ ሳይሆን መንገዱ ለሳይንስ ግኝት አመቺ ይሆናል። በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በፕሮቴስታንቶችና በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች መሀከል የጦፈ ትግል ከተካሄደ በኋላ የመጨረሻ መጨረሻ በአሸናፊነት መውጣት የቻለው የከበርቴው መደብ ነው። በመሆኑም አዳም ስሚዝና ሪካርዶ በጊዜው የበላይነትን የተቀዳጀው የከበርቴው መደብ አፈቀላጤዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

ከዚህ ስንነሳ ፖለቲካ የአገር መገንቢያ መሳሪያ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት የሚችለው ከረጅም ጊዜ ሂደት በኋላ ብቻ  ነው። ቀስ በቀስ ከታች ወደ ላይ እያደገ የሚመጣ ሲሆን በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ ግፊት እስከሌለ ድረስ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የፖለቲካን ትርጉም በማጣመም ጭቆናዊ አገዛዝን እንደሚያስፍኑ ነው። የድህነትና የበሽታ ምንጮች እንደሚሆኑ ነው። ለዚህ ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ዲስፖቲያዊ አገዛዝን በመቃወም የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና የሊበራል አስተሳሰብ እንዲስፋፋ እልክ አስጨራሽ ትግል የተካሄደው። ይህ ዐይነቱ በሳይንስና በፍልስፍና እንዲሁም በኢኮኖሚ ቲዎሪ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ሰፋ እያለ ከመጣው በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲታከልበት ስልጣንን ለተቆናጠጠው ኃይል በፍጹም መፈናፈኛ ሊሰጠው አልቻለም። ይህ ሁኔታ ለመድበለ-ፓርቲና ሰፋ ላለ በተለያየ መልክ ለሚገለጽ የፖለቲካ አስተሳሰብና የማህበራዊ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። በኢኮኖሚው መስክ የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣው የከበርቴው መደብም እንደፈለገው በመንግስትና በፖለቲካው ላይ የራሱን ጥቅም ብቻ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በጣም የጠለቀና ሰፋ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ምሁራን ብቅ በማለት የማህበራዊ አጀንዳዎችን ማንሳትና ማስተማር ይጀምራሉ። በተለይም በጊዜው በሳምንት ከሃምሳ ሰዓት በላይ ለሚሰራውና ለሚበዘበዘው የወዝ-አደር መደብ ንቃተ-ህሊናው እንዲዳብርና ለመብቱ እንዲታገል አመቺ ሁኔታ ፈጠሩለት። የተገለጸላቸው ምሁራንም በምንም ዐይነት ለጊዜው ኃያልነትን ለተቀዳጀው የህብረተሰብ ኃይል ሳያደሉ የማህበራዊ ጥያቄዎችን በማንሳትና የሰፊው ህዝብ ኑሮ እንዲሻሻል በፖለቲካው መድረክ ላይ ከፍተኛ ግፊት በማድረግ የሰፊው ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ቀስ በቀስ እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማበርከት ቻሉ። እነዚህ ሁሉ በመደመር ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፖለቲካ ለሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ከፍተኛ ትርጉም የሰጡትና ስልጣንን በጨበጡና በሰፊው ህዝብ ዘንድ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ የበቁት። ስለሆነም ፖለቲካ ሳይንሳዊና የአገር መገንቢያ መሳሪያ ሊሆን የበቃው በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ ለመመርኮዝ በመቻሉ ብቻ ነው። በጊዜው ፍልስፍና ወደ ሬል ፖለቲካ የሚቀየር ሳይሆን የግዴታ አንድ አገር በጸና መሰረት ላይ መገንባት አለበት የሚለው መመሪያ በመሆኑ ይደረግ የነበረው ርብርቦሽ ፖለቲካን የበለጠ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት መስጠት ነበር።  ስለሆነም በተቻለ መጠን ኃይል ሊሰበሰብ የሚችልበትን መንገድ መፈለግና ንቃተ-ህሊናን ማዳበር ነበር። የሞናርኪዎችም አካሄድ አንዱ ከሌላው በመኮረጅ ተሽሎ መገኘት ስለነበር ለአውቂዎችና አገርን ለመገንባት ለሚችሉ የዕደ-ጥበብ ሰዎች ቅድሚያ መስጠትና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበር።

ወደኛ አገር ስንመጣ ግን ያለው ችግር የፖለቲካን እንቅስቃሴ የጀመሩ ኃይሎች ብዙ ውጣ ውረድን በማሳለፍና ልዩ ልዩ መጽሀፎችን በማንበብና በመራመር ሳይሆን ተጨቁነናል በማለት ብቻ በስሜት በመገፋፋት ነው ትግል ማካሄድ የጀመሩት። አነሳሳቸው የህብረተሰብን ዕድገት ውጣ ውረድና አስቸጋሪነት በመረዳትና፣ በተለይም ደግሞ ባህል የሚባለው ነገር በፖለቲካ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አልነበረም ትግላቸውን የጀመሩት። በተለይም በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምህራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር አገዛዞች የጥገና ለውጥ ለማድረግ እንደሚሳናቸው በአብዛኛዎቹ፣ በተለይም ደግሞ የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ነን በሚሉ እንቅስቃሲዎች ዘንድ ግንዛቤ የገባ አልነበረም፤ አይደለምም። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብንና የባህልን ሁኔታ ያላከተተ የትግል ዘዴና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው እንቅስቃሴ ለአክራሪነትና ለአገር አውዳሚነት አመቺ ሁኔታ መፍጠር ቻለ። በተለይም በግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን ሰተት ብሎ የገባው ጥራዝ ነጠቅ ትምህርት ለእነዚህ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ፈጠራላቸው። ጭንቅላታቸውን ከማሾልና በሰፊው እንዲያስቡ ከማድረግ ይልቅ እልክ ውስጥ በመግባትና የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን ጠቅላላውን ህዝብ ማመስና መውጫና መላወሻ እንዲያጣ አደረጉት። ባጭሩ በተለያየ የታሪክ ወቅት ብቅ ያሉት አገዛዞች ሰፋ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍና መመሪያም ማግኘት ባለመቻላቸው በየጊዜው መወሰድ የሚገባውን ኢኮኖሚያዊና የፖለቲካ ጥገናዊ ለውጥ ማድረግ አልቻሉም። ራሳቸውም በጊዜው ሰፍኖ የነበረው የባህል ኋላ-ቀርነት ሰለባ በመሆናቸው ጠቅላላውን ህዝብ እንዴት እንደሚይዙና እንደሚያስተዳድሩ፣ ቀስ በቀስም ከታች ወደ ላይ ሊያድግ የሚችል ህብረተሰብአዊ ሀብት(National Wealth) እንዴት ሊፈጠር እንደሚችል የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይህ ማለት ግን በፍጹም ሙከራ አያደርጉም ማለት አልነበረም። የአፄ ቴዎድሮስን ጥገናዊ ለውጥ ሙከራና፣ በኋላ ደግሞ የሸዋ ነገስታት የዕደ-ጥበብ ሙያተኞችን ለማደራጀት ያደረጉትን ሙከራ በጥቂቱ ሊጠቀስ የሚችል ነው።  ያም ሆነ ይህ በአጠቃላይ ሲታይ በጊዜው የነበረው የፖለቲካ ክፍተት ከነበረው በጣም ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊናና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ያለመኖር ጋር የሚያያዝ እንጂ የተማሪው እንቅስቃሴና የብሄረሰብ ነፃ አውጭዎች ነን እንደሚሉት ሆን ተብሎ አገሪቱ የብሄረሰብ እስርቤት እንድትሆን የተደረገ የፖለቲካ ስልት አልነበረም። በተለያየ የታሪክ ወቅት ብቅ ብቅ ያሉት ነገስታቶች ልክ እንደ አውሮፓውያን ነገስታት በሃማኖት የሚመሩና የሚያምኑ፣ እንዲሁም ግዛቶቻቸውን ለማስፋፋት ትግል የሚያደርጉ ነበሩ። ስለሆነም የኛው የተለየና በጣም ጨቋኝ ተደርጎ የሚወሰድበት ምንም ምክንያት የለም። በጊዜው የተደረጉት ስህተቶች በሙሉ በጊዜው የነበረው በጣም ዝቅተኛ የሆነ ንቃተ-ህሊናና የፖለቲካ አስተሳሰብ ነፅብራቆች ናቸው። የነቃ የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ ትንሽ የኃይል አጠቃቀም ጉዳይ አመዝኖ ሊሆን ይችላል። አብዛኛው ጦርነት ደግሞ ይካሄድ የነበረው በመሳፍንታትና በነገስታት መሀከል በመሆኑ ሳይወድ በግድ ገበሬው ሰለባ ሊሆን በቅቷላ። አብዛኛው ጦርነት የሚካሄደው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት ስለነበር ብዙ በደል ይደርስ የነበረውም አማራ እየተባለ በሚጠራው አርሶ አደር ላይ ነበር።  ያም ሆነ ይህ የህብረተሰብ ህግ ብለን እንቅበለው ወይም አንቀበለው አንድ ማህበረሰብ ባለበት ረግቶ እንደማይቆይና እየተሰፋፋና እየተሳሰረ ለመሄድ እንደሚችል ከአገራችንም ሆነ ከሌሎች አገሮች መማር እንችላለን።  ጦርነትና ኃይል፣ እያደገ የሚመጣ የስራ ክፍፍልና የንግድ ልውውጥ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ገንዘብ የመገበያያ መሳሪያ መሆን፣  …ወዘተ.  በአንድ አገር ውስጥ እዚህና እዚያ ተሰበጣጥሮ ይኖር የነበረው በመሰባሰበና ልዩ ልዩ ግኑኝነቶችን በመፍጠር ወደ ማህበረሰብነትና ወደ ህብረተሰብ ይሸጋገራል። ይህ ተፈጥርአዊ ህግ በመሆኑ ማቆም በፍጹም አይቻልም። መነሳት ያለበት ጥያቄ እንዴት አድርገን ስርዓትና መልክ ልንሰጠው እንችላለን? በሚለው ላይ መረባረብ እንጂ የየራሳችንን ጎጆ በመቀልበስ አትድረሰብኝ፣  ይህ የኔ ብቻ ነው፣ ስለሆነም ልትጠቀምበት አትችልም እያልን የኋሊት ጉዞ ለማድረግ መታገል የህብረተሰብ ህግን እንደማጨናገፍ ይቆጠራል።

የህብረተሰብን ዕድገትና የህብረ-ብሄርን አነሳስና አስፈላጊነት የመረዳት አስቸጋሪ ጉዳይ ነው !

ለዲሞክራሲያዊ ነፃነት እንታገላለን በማለት ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉ ድርጅቶች ዋናውና  ተቀዳሚው ተግባር የአንድን ህብረተሰብ ውስጣዊ ህግጋትና የህብረ-ብሄርን አስፈላጊነት መረዳት ነው። እንደኛ ባለ በኢኮኖሚ እጅግ ወደ-ኋላ በቀረና፣ ለአንድ ህዝብ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች በማይገኙበት ወይም በማይሟሉበትና፣ የስራ ክፍፍል ባልዳበረበት አገር መቅደም ያለበት ጉዳይ እነዚህን ጥያቄዎች እያነሱና ምክንያቶታቸውን እያጠኑ መፍትሄ መፈለግ ነው። ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገውም ትግል በነዚህ ዙሪያ የሚሽከረከር መሆን ያለበት ሲሆን፣ እነዚህን እያነሱ የማያወያዩና መፍትሄም ለመጠቆም የማይችሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጨረሻ መጨረሻ ራሳቸው መልሰው የዕድገት መሰናክል ይሆናሉ። በአገራችን የፖለቲካ ትግል ታሪክም ውስጥ ያለው አስቸጋሪው ጉዳይ ለአንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ መገንባትና መጠናከር በሚያስፈልጉ መሰረተ ሃሳቦች ላይ ለመወያየት ልምዱና ፍላጎቱ ያለመኖሩ ነው። ለስልጣን የሚደረገውም ትግል ሁልጊዜ የማህበራዊና የህብረተሰብ ጥያቄዎችን ሲያካትት አይታይም። ይህ ዐይነቱ ችግር በሌሎች እንደ ብሄረሰብ ነፃነትና „ከጭቆና መውጣት“  አለብን በሚሉ የትግል መፈክሮች በመዋጥ መሰረታዊ የትግል ስልትና ለአንድ ህዝብ ተሳሰሮ መኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች እንዲረሱ ለማድረግ ተችሏል። በአገራችን ያለውን የተወሳሰበ የፖለቲካ ችግር ስንመለከት የሁሉም አትኩሮ በብሄረሰብ ዙሪያ የሚሽከረከር ነው። ሁላችንም የሚያሳስበን አገራችን ልትበታተን ትችል ይሆናል የሚለው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በመሰረቱ ግን እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር በቀላሉ የምትበታተን አይደለችም። ይህ ጉዳይ የውጭ ኃይሎች ህልምና ዓላማ ቢሆንም የህዝባችን በጋራ የመኖር ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑምና በብዙ ባህላዊ ጉዳዮችና እሴቶች የተሳሰረ ስለሆነ ይህንን እንደ ዋና አደጋ አንስቶ መከራከሩ ከመሰረታዊ የማህበራዊ ጥያቄዎች እንደመሸሽ ይቆጠራል። በሌላ ወገን ያለው ህብረተሰብአዊ ትርምስ፣ ማለትም ድህነትና ኋላ-ቀርነት የህብረተሰብአችን ዋና መለያዎች በመሆን ለብዙ ዐመታት እያተራመሱን እንደሚኖሩ መካድ አይቻልም። ያም ሆነ ይህ የብሄረሰብ ጥያቄን እያነሱ በሱ ላይ መፋለጡ የአገራችንን ህዝብ ሊያስተሳስር የሚችል በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዴት መገንባት እንዳለብን ከመወያየትና ከማጥናት ያግደናል። አንዳንድ አክራሪ የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ድርጅቶች ተወካይ ነን የሚሉትም የሚፈልጉት ይህንን ነው።  የህዝባችንን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለመፍታትና ለሁሉም ዜጋ እኩልነትን ሊያስፍን የሚችል ስርዓት ለመፍጠር ከመታገል ወይም መልስ ከመፈለግ ይልቅ በሆነው ባልሆነው መነታረክና ይህንን የትግል አርማ ይዞ መንቀሳቀስን ነው እንደ ዋና ፈሊጥ አድርገው የያዙት። ሳይንሳዊውና ፍልስፍናዊው መንገድ፣ በአጭሩ አገርን የመገንባቱ ጉዳይ አስቸጋሪ በመሆኑና ብዙ የጭንቅላት ስራንም ስለሚጠይቅ፣ ወደ ማያደክመውና ወደ ማያስጨንቀው ነገር ላይ ማትኮሩ የበለጠ ዝናን የሚያመጣ የሚመስላቸው ጥቂት ኃሎች አይደሉም። ሳይሰሩ ገንዘብ ማግኘትና ዝናን ማትረፍ የኑሮ ፈሊጥ በሆነበት ዘመን እያምታቱና ህዝብን እያጫረሱ መኖር የሚያዋጣው መነገጂያ መንገድ ሆኗል።

የብሄረሰቦች ተወካዮች ነን እያሉ እዚህና እዚያ ትግል እናካሄዳለን ብለው የሚንቀሳቀስ ኃይሎች የሚያነሱትን የመብትን መረገጥና የነፃነት መውጣትን ጉዳይ ስንመለከት በደንብ የማያጤኗቸው አያሌ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ለብሄረሰብአችን መብት እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ምን ዐይነት አገዛዝና መንግስታዊ መኪና በአገራችን ምድር ስፍኖ ነበር የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት በፍጹም አይቃጡም። አነሳሳቸው በጊዜው ስልጣንን የጨበጠው መደብ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣና በተለይም ኦሮሞዎች የሚገባቸውን ቦታ ስላላገኙ ይጨቆኑ ነበር የሚል ነው። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ አባባል ሳይንሳዊ አይደለም። በጊዜው አንድን ብሄረሰብ የሚወክል አገዛዝ ሳይሆን አነሰም በዛም መደባዊ ባህርይ ያለውና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚጠብቅ አገዛዝ ነበር በኢትዮጵያ ምድር የሰፈነው። የላይኛው አባባል ትክክል ቢሆን ኖሮ አባዛኛው የአማራ ክልል በጊዜው ክፍለ-ሀገር እየተባለ የሚታወቀው በዕድገት በተጥለቀለቀ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ የፊዩዳሉ ስርዓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት የስምንት መቶ ዐመት ዕድሜ ሲኖረው፣ ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ግዛት የተስፋፋው በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ነበር። ይህም ማለት ብዝበዛውና ጭቆናው በሰሜኑ ክፍል ያየለ ነበር ማለት ነው። በስምንት መቶ ዐመታት የብዝበዛ ዘመን የአማራውን ገበሬ እንዳያድግ አንቀው የያዙት እንደባህል የተወሰዱ መዐት የጭቆና መሳሪያዎች ነበሩ። አንደኛውና ዋናው የጭቆና መሳሪያ ማህበራዊ እንቅስቃሴ(Social Mobility) አለመኖሩ አማራውን በዕድገት እንዳይመነጥቅ አድርጎታል። በሶስተኛ ደረጃ የሚነሳው ጥያቄ በተለይም ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጡ ልጆች የመማርና ከፍተኛ ቦታ የመድረስ ዕድል ሲሰጣቸው በተለይም ኦሮሞዎች ይህ ዕድል ተነፍጓቸዋል የሚል ነው። ይህ ትልቁ ውሸት ነው። ዛሬ ሜዳውን የያዙት የነፃነት ታጋይ ነን ባዮችና የቀድሞው የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት መሪዎች ትምህርት ቤት የገቡና ዩኒቨርሲቲ ከጨረሱ ወይም ካቋረጡ በኋላ ወደ „ነፃነት ትግላቸው“  ያመሩ ነበሩ። የተጨቆኑ ቢሆኑና የመማር ዕድል ባያገኙ ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ ባልደረሱ ነበር። አውሮፓና አሜሪካም ባልመጡም ነበር። ተጫባጭ ሁኔታዎችን በሚገባ ከሳይንስ አንፃር በማንበብ የማይታዩና የማይገመገሙ ጉዳዮች ኃይል መጨረሳቸው ብቻ ሳይሆን የድህነትና የረሃብ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ለአጠቃላይና ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት መደረግ ያለበት ትግል እንዲዘነጋ ይደረጋል።

ያም ሆነ ይህ ለብሄረሰብ ነፃነት እንታገለለን የሚሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያለባቸው ከፍተኛ ጉድለት አንድ ብሄረሰብ ከሌላው ጋር ሳይቀላቀል በራሱ ባህል ብቻና አስተሳሰብ በመመራት እንደሚጓዝ ነው።  አንድ አስተሳሰብ ወይም ህሊናዊ አወቃቀር ስለሚኖረውም ይህ ሁኔታ ለዝንተ-ዓለም የሚቆይ ይመስላቸዋል። ይህ አስተሳሰብ የሚመነጨው የአንድን ግለሰብም ሆነ ብሄረሰብ ወይም ህብረተሰብ ውስጣዊ ኃይል(Dynamism) ካለመረዳት የተነሳ ነው። በተለይም ለፖለቲካ ስልጣን ወይም ነፃነት እንታገላለን እያሉ የሚሆን የማይሆነውን የሚያወሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚሰሩት የታሪክ ወንጀል የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ስለማይረዱ ነው። በዚህ ዐይነቱ አስተሳሰባቸው ራሳቸው ለኋላ -ቀርነት ዋናው ምክንያት ይሆናሉ። ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዳይዳብሩ እንቅፋት ይሆናሉ። ነፃነትን ከማምጣት ይልቅ የነፃነት እንቅፋት በመሆን እንታገልለታለን የሚሉት ህዝባቸው ዝንተ-ዓለሙን ፍዳውን እያየ እንዲኖር ያደርጉታል።

የተፈጥሮ ህግ ሆኖ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል አለው። ተንቀሳቃስሽም በመሆኑ አንድ ቦታ ረግቶ የሚኖር አይደለም። ስለሆነም ቀስ በቀስ እያለ ራሱን ማግኘት ሲጀምርና የስራ ክፍፍል ሲያዳብር የግዴታ ሌላ አካባቢ ከሚኖረው ህዝብ ጋር ይገናኛል። ሰው እንደመሆኑ መጠን በመቀራረብ የራሱን ባህልና ልምድ ያካፍላል፤ ከሌላውም ይማራል። በዚህ ዐይነቱ የተለያዩ ኮሙኒቲዎች ወይም ብሄረሰቦች ግኑኝነት ልዩ ዐይነት የሆነ ውስጠ-ኃይል ይፈጠራል። ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር በፈቃድ የሚካሄድ ነው ማለት አይደለም። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ኃይልና ጦርነት የየራሳቸው አስተዋፅዖ አላቸው። አንደኛው ላቅና ጠንከር ብሎ የሚገኘውና፣ የተሻለ አደረጃጀት ያለው የህብረተሰብ ኃይል ሌላውን በማስገበር በቁጥጥሩ ውስጥ ያደርጋል። ይህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ስብጥርና በኃይል አማካይነት አንዱ ሌላውን በራሱ ቅጥጥር ስር ማድረግ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደ ነው።፡ይህም ማለት ይህ ዐይነቱ አካሄድ „የተፈጥሮ ህግ“ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ይህ ባይሆን ኖሮ ቋንቋዎችና ፊደሎች፣ ባህሎች፣ የስራ ክፍፍሎችና ልዩ ልዩ ነገሮች መዳበር ባልቻሉም ነበር። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ አንድ ብሄረሰብ ሁሉን ነገር ራሱ አፍልቆ ብቻውን ያደገና የመነጠቀ የለም።  በአገሮች ውስጥ የባህልና የሳይንስ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በመመሰጣጠርና በመጋባትና በመዋለድ ብቻ ነው። ይህን ዐይነቱን አካሄድ የማይከተሉ ዘላኖች ወይም በከብት እርባታ ብቻ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ናቸው። እነሱም ቢሆኑ አንድ ቦታ ላይ የአኗኗር ስልታቸውን መቀየር አለባቸው። የተፈጥሮ ሃብት ውስን በመሆኑ በከብት እርባታና በግጦሽ  ብቻ ሊኖሩ አይችሉም። አንድ ቦታ ላይ የቲክኖሎጂ ለውጥ በማድረግ ወደ ተሻለ የአመራረት ስልትና የአኗኗር ዘዴ መሸጋገር አለባቸው። በሌላ አነጋገር በየጊዜው በተፈጥሮ ውስጥ በሚከሰት የዝናብ እጦትና ድርቅ የተነሳ ከብቶቻቸውም ሆነ ራሳቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይወዳቃሉ። በግጦሽና በምግብ እጦት የተነሳ ለሞት ይዳረጋሉ። በአንድ አካባቢ ተሰባስበው ኩሞኒቲ ካልመሰረቱና በተሻለ የምርት መሳሪያ ልዩ ልዩ ለምግብ የሚሆኑ ምርቶችንና ፍራፍሬዎችን ለማብቀል እስካልቻሉ ድረስ በየጊዜው የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ ይሆናል።  ከዚህ ዐይነቱ የተፈጥሮ ወላዋይነት ሊላቀቁ የሚችሉት ከሌላው ኮሙኒት ጋር ሲገናኙና በሳይንስና በቴክኖሎጂ እየተመሩ በተፈጥሮ ላይ የተወሰነ ቁጥጥር ማድረግ ሲችሉና፣ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ጥሬ-ነገሮችን ለጠቀሜታ እንዲሆናቸው መለወጥ ሲችሉ ብቻ ነው።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው ? አንድ ህዝብ ወይም ብሄረሰብ እንዲያድግ ከተፈለገ ካለበት ሁኔታ ተሻግሮ መሄድ መቻል አለበት። ከተተበተበበት ኋላ-ቀር የባህል ሰንሰለት መላቀቅ መቻል አለበት። የኔ ብቻ ነው ከሚለው አስተሳሰቡ በመላቀቅ ከሌላውም መማርና መቅሰም መቻል አለበት። ይህ ብቻ ሲህን ግለሰብአዊ ነፃነትን መቀዳጀት ይችላል። አዳዲስ መሳሪያዎችን በመፍጠር ሰው መሆኑን ያረጋግጣል። በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረው ያደርጋል። የመንፈስ እርካታን ማግኘት ይችላል ማለት ነው። ለብሄረሰብ ነፃነት እንታገላለን የሚሉ ወይም የግዴታ የፖለቲካ ስልጣን ለእኛ ነው የሚገባው ብለው እዚህና እዚያ የሚራወጡ ኃይሎች ችግር የህብረተስብን ውስጠ-ኃይል ለመረዳት አለመቻል ነው። አንድ ብሄረሰብም ሆነ ህብረተሰብ እንደ ፈሳሽ ውሃ ናቸው። ባለበት ረግተው የሚቆሙ አይደሉም። ሃይቅ እንኳ በነፋስ ኃይል ይንቀሳቀሳል። ስለሆነም ሳይወዱ በግድ አንደኛው ከሌላ ጋር በመጋባት ወይም በንግድና በስራ አማካይነት በመገናኘት ወደ ህብረተሰብ አመሰራረት መለወጡ የተፈጥሮ ህግ ጉዳይ ነው። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የሰዎች ርስ በርስ ግኑኝነትና ውህደት እንዲሁም በስራ ክፍልል ተሳትፎ የንግድ ልውውጥ ማድረግ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ይሸጋገር ዘንድ በጥናትና በዕቅድ መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል። አንድን ህብረተሰብ ህብረተሰብ የሚያሰኘው ተዝረክርኮ በመኖሮ ሳይሆን በታቀደና በደንብ በተገነባ ከተማ ወይም መንደር ውስጥ ስርዓት ባለው መልክ ሲኖር ብቻ ነው። ከተማዎች እንደ እየአስፈላጊነታቸው ለመኖሪያ፣ ለመገበያያ፣ ለመዝናኛ፣ ለመስሪያ ቤቶች፣ ለቡና ቤቶችና ለመጽሀፍት ቤቶች እየተባሉ የሚሰሩና በስነስርዓት የሚታቀዱ ከሆነ በዚያ የሚኖረውም ማንኛውንም ሰው ደስታን ይጎናጸፋል።  ከዚህም ባሻገር ለመኖር የሚያስፈልጉ እንደ ንጹህ ውሃና፣ መብራትና መቀቀያ፣ እንዲሁም መታጠቢያ  የመሳሰሉትን መሰረታዊ ነገሮች ካገኘ እንደዚህ ዐይነቱ እንደ ህብረተሰብ ሊታይ ይችላል። በስርዓት የመኖሩ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አካባቢው ውብ ሆኖ ከተሰራ የመፍጠር ኃይሉም ከፍ ይላል። የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገት ለተመለከተ የመጀመሪያዎቹ ተመራማሪዎች እንደነ ጋሊሊዮ የመሳሰሉት የመፍጠር ኃይል ማግኘት የቻሉት በጊዜው የዕደ-ጥበብ ስራና ንግድ እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴ በሰፈነበትና በተዘጋጀበት ከተማ ውስጥ ተወልደው በማደጋቸው ነው። በጊዜው የነበረውም ሁኔታ ለምርምር የሚያመች ነበር። እንደዛሬው ዓለም በኢንፎርሜሽን የተጥለቀለቀ ባለመሆኑ ጭንቅላትን የማወናበዱ ኃይል አልቦ ነበር ማለት ይችላል። ስለሆነም ስለህብረተሰብ አስፈላጊነት ወይም አንድ ህዝብ በአንድ አካባቢ ተሰባስቦ ስለመኖሩ ጉዳይ ስናወራ አያሌ ነገሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን ማለት ነው።

የአገራችንን የህብረተሰብ ታሪክ የላይ የላዩን በምንመረምርበት ጊዜ ከላይ በተተነተነው መልክ ህብረተሰብአችንን ሊያደራጀው የሚችል መንግስታዊም ሆነ ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ እንደ ማህበረሰብና እንደ አንድ ውስጣዊ ኃይል እንዳለው ማህበረሰብ(Social Being) ሊገነባ አልቻለም። በተለይም ኢትዮጵያ በአንድ ማዕከላዊ አገዛዝ ስር ስትጠቃለል ጊዜው አመቺ ቢሆንም ሁኔታውን ለመጠቀም የሚችል ህብረተሰብአዊ ኃይል ባለመኖሩ ህዝባችንን እንደህብረተሰብ ማደራጀት አልተቻለም። የኋላ ኋላ ካፒታሊዝም ተቦጫጭቆ ሲገባ ከተማዎችና መንደሮችን በዕቅድ ከመሰራት ይልቅ ወደ ቆሻሻነት ተለወጡ። ህዝቡም አለኝታ የሚሆነው መንግስት ወይም አገዛዝ ስላልነበረው ፍላጎቱንና ምኞቱን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም። ይህ ዐይነቱ የከተማዎች መዝረክረክ በኛ አገር ብቻ ጎልቶ የሚታይ ሳይሆን በጠቅላላው የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች ችግር ነው። ከ1950ዎቹ  ዓ.ም ጀምሮ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የምትክ ኢንዱስትሪ እየተባለ የተተከለው ብዙ አገሮችን ማቀጨጩ ብቻ ሳይሆን አርቆ አሳቢና ተመራማሪ የሆነ የህብረተሰብ ኃይል እንዳይወጣ ለማድረግ በቃ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአንድ በኩል በከተማዎች ውስጥ አቀባባይ ከበርቴና ቢሮክራሲያው መደቦች ሲፈጠሩ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሴተኛ አዳሪነት፣ ማጅራት መችነትና የጫማ ጠራጊነት(ሊስትሮ) ህይወትን ማሸነፊያ ዘዴዎች ተደረገው ሲወሰዱ፣ በዚያው መጠንም የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች(Slums) በመስፋፋት አጣቃላዩን የህብረተሰብ ግንባታ አካሄድ ማጣመም ተቻለ። ይህ ዐይነቱ የተበላሸ የአኗኗር ሁኔታ ከሁሉም ብሄረሰብ የመጡ የአገሪቱን ዜጎች የሚመለከት ነበር። በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ የተስፋፉ የቆሻሻ መኖሪያ አካባቢዎችን ለተመለከተ በእነዚህ ቦታዎች ከሁሉም ብሄረሰቦች የተውጣጡ የሚኖሩበት ነበር፤ አሁንም ነው። ይህ ጉዳይ ከአገሪቱ በጣም ደካማ ከሆነ የኢኮኖሚ አወቃቀር ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ ተከታታይና ጥሩ የወር ገቢና አስተማማኝ የስራ ቦታ የሌለው የግዴታ በእንደነዚህ ያሉ ቆሻሻ ቦታዎች እንዲኖር ይገደዳል ማለት ነው። ነገሩን ከፍትሃዊ የአስተዳደር ጉድለት፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግን ካለመገንዘብና፣ አንድ ህብረተሰብ እንደህብረተሰብ እንዲታይ ከተፈለገ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ነገሮች በስራ ላይ ባለመዋላቸውና፣ እነሱንም ካለመረዳት የመነጨ ነው። ከሶስይሎጂ አንፃር ሲታይ በጊዜው የተፈጠረው ሁኔታ የተወሰነውን በአሪስቶክራሲውና በቢሮክራሲው መደብ ውስጥ የሚጠቃለለውን መደብ ተብሎ የሚጠራውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ሲጠቅም፣ አብዛኛው በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተገዷል ማለት ነው።  ስለሆነም በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በሶስይሎጂ መነጽርና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግን መሰረት ሳያደርግ ተግባራዊ የሆነውን ኢሳይንሳዊ አካሄድ በብሄረሰብ መነጽር ማየትና ማተት በፍጹም አይቻልም። ብሄረሰብ የሳይንስ ወይም  የዕውቀት አካል ባለመሆኑ የአንድን ህብረተሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያቶቻቸውን ማወቂያና መተንተኛ ዘዴ በፍጹም ሊሆን አይችልም።

ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የብሄረሰብ ነፃነትን አርማ ይዘው የሚታገሉ ኃይሎች ዘንድ ያለው ችግር የአንድን አገር የውጣ ውረድ ጉዞና የህብረተሰብ አገነባብ ችግር ለመረዳት አለመፈለግ ነው። ጊዜ ወስዶ ለማጥናት ካለመሻት የተነሳና በተለይም በውጭ ኃይሎች መካሪነት በመደለል ወደ አላስፈላጊ ድምደማ ላይ በመድረስ አንድን ህብረተሰብ በአንድ ትውልድ ብቻ ሳይሆን በሁለትና በሶስት ትውልድ ሊወጣው የማይችልው ችግር ውስጥ ይከቱታል። ተፈጥሮአዊ የሚመስለው የህብረተሰብ አገነባብ ሂደት በዘመናዊነት መነጽር እየታየ በየጊዜው ለመሻሻል ባለመቻሉ የተነሳ ምስቅልቅል ሁኔታ እንደተፈጠረ የብሄረሰብን አርማ አንግቦ ነፃ መውጣት አለብኝ ብሎ ለሚታገለው ብቻ ሳይሆን ለራሱም የአንድነትን ወይም የብሄራዊ ነፃነቴ መከበር አለበት ለሚለው ኢትዮጵያዊ ኃይል ሁኔታው ይህንን ያህልም ግልጽ ሊሆንለት የቻለ አይመስለኝም።

ስለሆነም በጊዜው ይህንን በሚመለከት የተፈጠረው ችግር ፖለቲካን የህብረተሰብ አገነባብ ሳይንሳዊ መሳሪያ አድርጎ ካለመረዳት የተነሳ  በመሆኑ ብቻ ነው። አንዱን ብሄረሰብ ለመጥቀም ብቻ፣ ሌሎችን ደግሞ ለመጉዳትና አቀጭጮ ለማስቀረት ሆን ተብሎ የተካሄደ ፓለቲካ በአገራችን ምድር አልተካሄደም። ይልቁንስ እንዲዚህ ዐይነቱ አካሄድ ባለፉት 26 ዓመታት ጎልቶ የሚታይ ነው። ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ የመንግስትን መኪና የጨበጠና ስትራቴጂክ የሆኑ የኢኮኖሚ መስኮችን የሚቆጣጠርና ሀብት የሚዘርፍበት ሁኔታ በግልጽ የሚታይበትን ሁኔታ ነው የምንመለከተው። ያም ሆነ ይህ ነገሩን በንጹህ መንፈስ ከፍልስፍና፣ ከሶስይሎጂ፣ ከከተማ ዕቅድና ከተፈጥሮ ሳይንስ፣ ከኢንስቲቱሽን አገነባብ፣ ባጭሩ በአጠቃላይ ሲታይ ከአገር ግንባታ አንፃር መመርመሩ በጊዜው በገዢው መደብና በአስተዳደሩ ውስጥ የነበረውን ከፍተኛ የአስተሳሰብ ክፍተትና ንዝህላልነት መረዳት ይቻላል። በዚህ መልክ ነገሩን ስንረዳ ወደፊት በምን መልክ ችግሩ እንደሚቀረፍና ጤናማ ህብረተሰብ መመስረት እንደምንችል ግልጽ ይሆንልናል ማለት ነው።

የወያኔ ፖለቲካ በፖለቲካ ሳይንስ መነፅር ሲገመገም !

የአንድን የገዢ መደብ ወይም ስልጣንን የጨበጠ አገዛዝ ፖለቲካ መረዳት የሚቻለው በሚያወጣውና ተግባራዊ በሚያደርገው አጠቃላዩ ፖሊሲ በመነሳት ነው። ፖለቲካ ለፖለቲካ ተብሎ የሚካሄድ ነገር ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ የዛሬውን ዕድሉንና የአኗኗር ስልቱን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ተከታታይ ትወልድ ህይወት የሚወስን ጉዳይ ነው። ፖለቲካ የሚባለው ከግሪክ የመነጨ ጽንሰ-ሃሳብ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም በአንድ ከተማ ወይም ከተማዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችንና መንግስት ከነዚህ ሰዎች ጋር ያለውን ግኑኝነትና የአስተዳደር ስልቱን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ስለሆነም አርስቲቶለስ ፖለቲካን የሳይንስ ሁሉ አለቃዎች ብሎ ይጠራዋል። በእሱም መሰረት ፖለቲካ መንግስትን ወይም አስተዳደርን፣ የቤተሰብ ጉዳይን፣ የተለያዩ የመንግስት ኢንስቲቱሽኖችንና ተግባሮቻቸውን፣ የሀብትን ጥያቄና ክፍፍልን፣ ባጭሩ አጠቃላዩን የሰውን ህይወት የሚያካትት ጽንሰ-ሃሳብ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የአንድ አገር አገዛዝ ፖለቲካ መለኪያው፣ በአገሩ ውስጥ በሚያካሂደው ፍትሃዊና ኢ-ፍትሃዊ ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የእርሻ ፖሊሲ፣ የማህበራዊ ፖሊሲ፣ የወጣቶችና የሴቶች ፖሊሲ፣ የከተማ አቀያየስና አገነባብ ፖሊሲ፣ በአገር ውስጥ ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎች ስለመፍጠሩና አለመፍጠሩ የሚመለከትን ጉዳይ፣ በተጨማሪም ብሄራዊ ነፃነትን አስመልክቶ ስለሚከተለው ፖለቲካና ከውጭ አገሮች፣ በተለይም ኃያላን መንግስታት ከሚባሉት ጋር ባለው ግኑኝነት የሚመዘን ነው። ባጭሩ ፖለቲካ የአንድን አገር ህዝብ ዕድልና ህይወት የሚወስን ሲሆን፣ ስልጣንን የጨበጠው መደብ አገዛዝ ታሪካዊና ማህበራዊ ግዴታ አገሩን በስነስርዓት ማስተዳደር ነው። በተቻለ መጠን ለህዝቡ አለኝታ መሆንና የተሟላ ነፃነት መስጠትና ማስከበር ነው። በሌላ አነጋገር፣ አንድ አገዛዝ በዚያ አገር ውስጥ በጣም ጥሩ ህገ-መንግስት ካለ ያንን ህገ-መንግስት ተከትሎ አገሩን የማስተዳደር ግዴታ አለበት ማለት ነው። አሁንም በሌላ አነጋገር አንድ አገዛዝ የህዝብ ተገዢና ታዛዥ እንደመሆኑ መጠን ስልጣንን ጨብጬአለሁ ብሎ እንደፈለገው አገሩን የማከረባበት መብት የለውም። ፕሬዚደንት፣ ጠቅላይ ምኒስተርና ሊሎች ምኒስተሮችም ስልጣንን ሲረከቡ የሚምሉት በህገ-መንግስቱ ነው። ይህም ማለት በተቻለ መጠን የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅና ጉዳት እንዳይደርስበት መከላከል ወይም ጉዳቱን በጣም መቀነስ ነው። በአውሮፓ ምድር ጠቅላይ ምኒስተሮችና ሌሎች ምኒስተሮች ስልጣንን ሲረከቡ የሚምሉት ህገ-መንግስታቸውን እንደ መነሻ በማድረግ ነው። ደስታውን ከፍ ማድረግ፣ ሀዘኑን ደግሞ መቀነስ አለብን እያሉ ነው። ስለመንግስትና ፖለቲካ የፃፉትን ታላላቅ ፈላስፋዎች ከፕላቶ ጀምሮ እስከ ዊሊሄልም ሁምቦልድት ድረስ የሚያስተምሩን የአንድ መንግስትና አገዛዝ ተግባር እኩልነትን ማስፈንና፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ማንነቱን ሊገልጽበት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብቻ ነው።  በስሜት ወይም የመንግስትን መኪና ጨብጬአለሁ ብሎ እንደፈለገው ሁሉን ነገር የሚያደርግ፣ ሰውን የሚገድልና የአገርን ሀብት የሚዘርፍና የሚያዘርፍ ይህ ዐይነቱ አገዛዘ እንደ መንግስትና እንደ አገዛዝ ሊቆጠር አይችልም።

ደጋግሜ እንዳልኩት አንድ አገር መጨፈሪያ አይደለም። እያንዳንዱ አገር ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ያለፈው ትውልድ ብዙ መስዋዕትነትን ከከፈለ ባኋላ ነው። በእርግጥ በተለያዩ የታሪክ ኢፖኮች በነበረው ንቃተ-ህሊና ማነስ የተነሳ በየጊዜው ስህተቶችና አልፎ አልፎ አንዳንድ ወንጀሎች ተሰርተዋል። የተከታታዩ ትውልድ ዋና ተግባር ግን በዚያን ጊዜ የተሰሩትን ስህተቶች እንደመነሻ በመውሰድ የቂም በቀል ፖለቲካ ማካሄድና አገርን ማከረባበት ሳይሆን፣ በየጊዜው የተሰራውን የፖለቲካ ስህተት ከሳይንስ አንፃር በመመርመር የተሻለና አገርን የሚያበለጽግና ህዝብን የሚያረጋጋ ፖለቲካ ማካሄድ ብቻ ነው። ስለዚህም ነው ፖለቲካ የአስተዳደር ጥበብ ነው የሚባለው። ይህንን የማይገነዘብ፣ የሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና ክንውናዊ መሆኑን የማይረዳና ለመለወጥና ለመሻሻል ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ እንደሚያስፈልገውና፣ ለዚህ ደግሞ በየጊዜው በትክክል ዕውቀት መኮትኮት እንዳለበት የማይገነዘብ አገዛዝ በቂም በቀል እየተነሳ አገርንና ህዝብን የሚያተራምስ ከሆነ ይህ ዐይነቱ አገዛዝ ተልዕኮው ሌላ ነው ማለት ነው። በዚህ ዐይነቱ የማተራመስና ህዝብን የመጨፍጨፍ ተግባሩ ደስታንና ጥቅምን የሚያገኝ ከመሰለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ያለው፣ ካሊያም ጭንቅላቱ የታመመ ብቻ ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ አገዛዝ አገርን እያተረማመሰና ራሱን ብቻ እያደለበ ለሺህ ዐመታት የቆየበት ጊዜ የለም። ይልቁንስ ለአገርና እወክለዋለሁ ላለው ህዝብ ከፍተኛ አደጋና ጠንቅ ጥሎላቸው ነው የሚያለፍው። ዛሬ የተጠቀመ የሚመስልው ከነገወዲያ ግን ልጆቹና የልጅ ልጆቹ መግቢያና መውጫ የሚያጡበትን ሁኔታ ነው ጥሎ  የሚያልፈው።

ወያኔ ስልጣንን ከመጨበጡ በፊትም ሆነ በኋላ ተግባራዊ እንዳደረገውና ዛሬም እንደምንመለከተው ከላይ ባጭሩ ለማመልከት የሞከርኩትን የፖለቲካ መንፈስ የተከተለና የሚከተል አይደለም። በአፀናነሱና በአስተዳደጉ ቂም-በቀልን መሰረት አድርጎ በመነሳቱ፣ ስልጣንን ሲጨብጥም ያንን እርኩስ ተግባሩን ነው ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው። ከክልል የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ተነስተን፣ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የተበየነውንና ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት(Structural Adjustment Program) አጠቃላዩ ፖለቲካው አገርን የሚያዳክም፣  ህዝባችን ርስ በርሱ እንዳይተማመን የሚያደርግ፣ የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም በአገር ግንባታ ውስጥ እንዳይሳተፍ፣ መሳሪያዎችን በመፍጠር በአገር የሀብት ግንባታ ውስጥ እንዳይሳተፍ ማድረግ…ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት የአገዛዙን የተበላሸ አስተሳሰብ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በምንም መልኩ ከፖለቲካ ጋር የሚያያዝ አይደለም። አገዛዙ እጠቀምባቸዋለሁ የሚላቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ መሳሪያዎች ሁሉ የመጨረሻ መጨረሻ አገሪቱን በሁሉም መስክ የሚያዳክሙ ናቸው። አገራችንና ህዝባችንን ለአደጋ የሚያጋልጡ ናቸው። አንድ ቀን በቀላሉ በውጭ ኃይል ለመወረር የሚያመች ሁኔታ ነው የዛሬው አገዛዝ ጥሎልን የሚያልፈው።

ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ ፖለቲካን ሳይንሳዊ የሚያሰኘው ልክ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ የአንድን ነገር አፈጣጠርና የመነሻውን ምክንያትና ይዘቱን መርምሮ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ አንድ ሳይንቲስት ከፍተኛ ጥናትና ምርምር እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ፖለቲከኛ ነኝ የሚልም በአንድ አገር ውስጥ በግልጽ የሚታዩና የማይታዩ ችግሮች ዋና ምክንያቶቻቸው ምንድነው?  ብሎ በመመርመር መፍትሄ ለመስጠት መሞከር ነው። በሌላ አነጋገር፣ ችግሮቹን ለማባባስ ሳይሆን የችግሩን ዋና መነሾ በመመርመር ተቀራራቢ መፍትሄ ለመስጠት መሞከርና ራሱም የማይችል ከሆነ ደግሞ ምክር መጠየቅ የአንድ አገዛዝ ግዴታ ነው። ከአውሮፓ የረጅሙ የፖለቲካና የአገር ግንባታ ታሪክ የምንማረው ፖለቲካ የሚባለው በአዋቂዎች የፈለቀና የተስፋፋ ሲሆን፣ ፖለቲካዊ ክንውኖችም ቀስ በቀስ ተግባራዊ መሆን የቻሉት ብዙ ምሁራን በመሳተፋቸው ነው።  ፖለቲካም ከሳይንስ፣ ከፍልስፍና፣ ከቲዎሎጂ፣ ከኢኮኖሚክስና ከአገር ግንባታ ጋር፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ከማህበራዊ ጥያቄ ጋር በመያያዙ የአውሮፓውን የፖለቲካ አካሄድ ለየት ያለና ሁለንታዊ ሊያደርገው በቅቷል። እንደ እኛ አገሩ ማወናበጃና ህብረተሰብን ማከረባበቻ መሳሪያ አይደለም ማለት ነው።

የወያኔን ፖለቲካና በተለይም የክልል ፖለቲካውን ስንመለከት ከተሳሳተ ግንዛቤ በመነሳት ነው ፖለቲካ አካሂዳለህ ወይም አገሪቱን አስተዳድራለሁ የሚለው። በእሱና በአንዳንዶች ዕምነት ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት መቶ ዐመታት በአንድ ብሄረሰብና ርዕዮተ-ዓለሙ ስትገዛ የነበረች ስለነበረች ሌሎች ብሄረሰቦች ደግሞ መብታቸው የተነፈገባት አገር ናት። ስለሆነም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የአማራውን የገዢ መደብና ርዕዮተ-ዓለሙንና ሌሎች እሴቶችን አንኮታኩቼ በመሰባበር አዲስ የብሄረሰቦች መብት የተከበረባትና በኢኮኖሚ ግንባታ የሚበለጽጉባት ህብረ-ብሄር ያልሆነች አገር መመስረት አለበት ብሎ ነው የክልል ፖሊሲውን ተግባራዊ  ማድረግ የጀመረው። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የተማሪው እንቅስቃሴም ሆነ ለብሄረሰባችን መብት እንታገላለን ብለው የተነሱት እንቅስቃሴዎች በሙሉ የብሄረሰብን ጭቆና እንደመታገያ ስልት ሲያደርጉና ሲያራግቡ ሰፋ ያለ የሶስዮሎጂና የህብረተሰብ ግንባታና አስቸጋሪ ጉዞ ታሪክ በፍጹም አላጠኑም። ከሌኒንና ከስታሌን የብሄረሰቦች ጥያቄና አተናተን ሁኔታ ብቻ በመነሳት ነው እዚህ ዐይነቱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የበቁት። የእነሱንም ትንተና ስንመለከት በጊዜው ከራሺያ ሁኔታ በመነሳት እንጂ የሌሎችን አገሮች  የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ በማጥናት አይደለም ቲዎሪያቸውን ለመንደፍ የቻሉት። ሊሆንም አይችልም። የስታሊንን የብሄረሰብ አተናተን ስንመለከት በአንድ ብሄረሰብ ውስጥ የሚጠቃለል ግለሰብ ሁሉ ተመሳሳይ ባህርይ፣ ፍላጎትና ህልም  ሊኖረው በፍጹም አይችልም። አንድ ወጥ አመለካከት ሊኖረው ይችላል ብለን እንኳ ብንቀበል ይህ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ሊታይ የሚችለው በስራ-ክፍፍል ባልዳበረ፣ ኢንስቲቱሽኖች በሌሉበት፣ በከብት እርባታ ብቻ በሚተዳደር ገና እንደ ማህበረሰብና እንደ ህብረተሰብ ባልተደራጀ ጎሳ ውስጥ ብቻ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ብሄረሰብ በየቀኑ ተመሳሳይ ከሆኑ ነገሮች ጋር ስለሚጋጭ ያንኑ ብቻ እንደባህሉ አድርጎ እንዲወሰድ ይገደዳል። አኗኗሩም ውስን ስለሚሆን ካለበት ሁኔታ በመነሳት ወደ ሚቀጥለው የዕድገት ደረጃ አይሸጋገርም። ይሁንና ይህ ዐይነቱ አተናተን የሰውን ልጅ ውስጣዊ ኃይል የሚፃረርና እዚያው ቀጭጮ እንዲቀር የሚያደርገው ነው። ባጭሩ የተማሪው እንቅስቃሴና የብሄረሰብ ነፃነት ታጋዮች አነሳስና መፈክር የህብረተሰብንና የሰውን ልጁ የውስጣዊ-ኃይል ክንዋኔና (Dynamic Process)  ዕድገትንና ስልጣኔን የሚፃረር ነው። ብሄረሰቦች መብታችሁ ብቻ ይታወቅ፣ የተወሰነ መሬትም በማግኘት በዚያው ጠግባችሁ መኖር ትችላላችሁ የሚልና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂን፣ ውብ ውብ የሆኑ የከተማ ግንባታዎችን፣ በአጭሩ የሰለጠነና የጠነከረ ህብረተሰብ የመገንባት አስፈላጊነትን የማያካትት አካሄድ የመጨረሻ መጨረሻ ነፃ ወጥተሃል፣ የፈልግከውን ነገር ማድረግ ትችላለህ ተብሎ የተበየነበትን ብሄረሰብ ነው የሚጎዳው። ይህንን ስል ጠቅላላውን የተማሪ እንቅስቃሴ ለመወንጀል ሳይሆን ፍላጎታቸውና ምኞታቸው ምናልባት ትክክል ቢሆንም፣ የትንተናው መነሻና ዓላማቸው የህብረተሰብ አገነባብ ሳይንስን የተከተለ እንዳልሆነ ለማሳየት ብቻ ነው። ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ አንድን አገር የሚያዳክም፣ አንዱ ብሄረሰብ ሌላውን እንዲጠረጥር የሚያደርግና በፍጹም እንደሰው እንዲታይ የሚያደርገው አይደለም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በብሄረሰብ ውስጥ የሚካለልና መብቱ ተጠብቋል የሚባለው ግለሰብአዊ ነፃነትን እንዳያገኝና ተቺ(Critical) ዜጋና በራሱ ላይ ዕምነት እንዳይኖረው ይደረጋል። ሰፋ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ እዚህና እዚያ እየተሯሯጠና ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመገናኘትና በመማር የመፍጠር ችሎታውን እንዳያዳብር ያግደዋል።

የወያኔዎች ፖለቲካ በመሰረቱ የብሄረሰቦችን መብት የሚያረጋግጥ ቢመስልም- በምንም መልኩ ያረጋገጠ አይደለም- ዋናው ዓላማው የከፋፍለህ ግዛን ፖሊሲ በመጠቀምና እዚህና እዚያ አዳዲስ የብሄረሰቦች „የገዢ መደቦች“(War Lords) በመኮትኮትና በማደለብ፣ በዚያም አማካይነት በወያኔ የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ በማካተትና በማኮላሸት፣ የትግሬን የበላይነት ማስፈን ነው። ባጭሩ አገሪቱ እየተዋከበችና ህብረተሰቡ ርስበርሱ እየተጠራጠረ፣ የወያኔ ካድሬዎች ደግሞ በየቦታው አባወራ በመሆን ህዝብን እያስፈራሩና ነፃነቱን እረግጠው በዚያው ቀጭጮ እንዲቀር  በማድረግ ለዝንተ-ዓለም የመግዛት ዓላማ ነው ያላቸው። በእኩልነት ስም የተካለለውን የየአካባቢውን ሁኔታ ስንመለከት ከኢኮኖሚና ከከተማዎች እንዲሁም ከመንደሮች ግንባታና ከሶሻል ፖሊሲ አንፃር ሁኔታ ስንመረምረው እያንዳንዱ ክልል የቀጨጨና፣ ስልጣንን የጨበጡ የየክልሉ መሪዎች ደግሞ በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ እንጂ የየብሄረሰቦቻቸው ዕውነተኛ ተጠሪዎች ያልሆኑና ችግሮቻቸውንም መፍታት የሚችሉ አይደሉም። በተቃራኒው ግን ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን የሚያስፋፉና የሚያጠናክሩ ናቸው። የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ተመጣጣኝና ሚዛናዊነት ያለው አጠቃላይ ሀብትን ሊፈጥር የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ሲከተሉ አይታይም። ከዚህ ስንነሳ የምንመለከተው ነገር በክልል ስም የሚካሄደው ፖለቲካ በመሰረቱ ከፖለቲካ ሳይንስ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለም። ዛሬ በአገራችን ምድር  የሰፈነው አገዛዝ ዘራፊና(Predatory State) ፋሺሽታዊ አገዛዝ ነው። በዚህ ፖሊሲው ደግሞ ጠቅላላው የምዕራቡ ካፒታሊስትና ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በሙሉ የሚተባበሩትና ግፋበት እያሉ አስፈላጊውን ርዳታ ይሰጡታል።

ወደ መንግስት መኪናው ስንመጣ ከወታደሩ የበላይ አካሎች፣ ከሴክዩሪቲውና ከፖሊስ የበላይ ሹማምንት ድረስ በወያኔ ሰዎች የተያዙ ወይም የአንድ ብሄረሰብ የበላይነት የሰፈነበት ነው።  የህግ አውጭውንም ወይም „የፓርሊያሜንቱን“ ጉዳይ ስንመለከት ተጠሪዎቹ መብትና ስልጣን የሌላቸው፣ ስልጣንን የጨበጠውን ኃይል ፍላጎት የሚያሟሉ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የገዢው መደብና የመንግስት መኪና እዚያው በዚያው የተቆላለፉ ሲሆኑ የህዝብ የመጨቆኛ መሳሪያዎች የሆኑና ሰፋ ያለና ግልጽ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን ህብረተሰቡን አንቀው የያዙ ናቸው። ይህም ማለት በወያኔ ዘመን ፖለቲካና የመንግስት መኪናዎች የጥቂት ሰዎች የግል ሀብት የሆኑና፣ አገርን እንደፈለገው መበዝበዣና ህዝብን ማደኸያ፣ እንዲሁም ኋላ-ቀርነትን ማስፋፊያ መሳሪያዎች ናቸው። ይህ ዐይነት ወደ ግል ሀብትነት የተለወጠ የመንግስት መኪና ደግሞ ስትራቴጂከ የሆነ የአገር ሀብቶችን የሚቆጣጠርና፣ እንደ ወርቅና ሌሎች ተፈላጊነት ያላቸውን የጥሬ-ሀብቶች በግልጽ ወደ ውጭ የሚያወጣ ነው። ባጭሩ የወያኔ አገዛዝ የመንግስትን መኪናና ፖለቲካውን በራሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ ሳያፍርና ሳይፈራ የህዝብን ሀብት እየዘረፈ የካፒታሊስት አገሮችን የሀብት ክምች አጋዥ ለመሆን የበቃ ነው። የእነሱ ተቀጢያና ታዛዥ እስከሆነም ድረስ ማንኛውንም ርዳታ ማግኘት እንደሚችል ያምናል። የኢምፔሪያሊስት አገሮችም ዋና ዓላማ እንደዚህ ዐይነቱን አገዛዝ በመደለልና አስፈጊውን ነገር እያደረጉለት አገራችን ከድህነት እንዳትላቀቅና ህዝቡም አቅመ-ቢስ ሆኖ እንዲኖር ማድረግ ነው። በሳይንስና በቴክኖሎጂ የበለጸገች አገር፣ በራሱ የሚተማመን ህዝብ የካፒታሊስትት አገሮች ጠንቅ ሆኖ ስለሚታያቸው እንደ ወያኔ ዐይነቱ አገዛዝ ከስልጣን እንዳይወርድ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያደርጉለታል። ይህም ማለት የሱ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በኢምፔሪያሊስት አገሮች የሚወሰን ነው ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ የወያኔ ፖለቲካ ከሳይንስ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። የህብረተሰብ ችግሮችን መፍቻ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ አዳዲስ ችግሮችን በመፍጠር ሁኔታውን ውስብስብ የሚያደርግ ነው። ለብዙ መቶ ዐመታት በቀላሉ ሊፈታና መልክ ሊይዝ የማይችል ጠንቅ ጥሎ ነው የሚያልፈው። ይህ ዐይነቱ አገዛዝ በኢምፔሪያሊስት የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ የተካተተና የእነሱን ትዕዛዝ እየተቀበለ ብሄራዊ ነፃነትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲገፈፍ ያደረገ ነው። የሶስት ሺህ ዐመቱ ታሪካችንና ጠላትን ከአንድም ሁለቴም በላይ ተዋግተን ነፃነታችንን የተቀዳጀንበት ሁኔታ በዚህ መልክ ሙሉ በሙሉ እንዲገረሰስ ሊደረግ በቅቷል።

በኔዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተውን ፖሊሲውን ስነመለከት ይህ ዐይነቱ የሞነቴሪ ፖሊሲ ባለፉት አርባ ዐመታት እንደተረጋገጠው በአንድ አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ሰፋ ባለ የማኑፋክቱር ግንባታ ላይ የሚመረኮዝ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ግንባታ እንዲገነባ የሚያደርግ አይደለም። የፖሊሲው አርቃቂዎችና ደንጋጊዎች፣ ማለትም፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጀትና(IMF) የዓለም ባንክ ዋና ዓላማ እያንዳንዱ የሶስተኛው ዓለም አገር ከውስጥ የተሳሰረ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ እንዲካሄድ ማድረግ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ ይዘትና ባህርይ የሌለው የሞነቴሪ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በመገፋፋትና ጭነት በማድረግ አንድን አገር ዕድገቷን መቅጨት ነው። በጣም ጥቂት ከሆነው በስተቀር አብዛኛው ህዝብ በድህነት እየታሸ አቅመ-ቢስ ሆኖ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ይህንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ከአገሮች ግንባታ አንፃር በማወዳደር አገር አፍራሽነቱን ማረጋገጥ ይቻላል። ጃፓንና ደቡብ ኩሪያ፣ እንዲሁም ምዕራብ ጀርመን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ኢኮኖሚያቸውን መገንባትና ጠንካራ ህብረተሰብ መመስረት የቻሉት በሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም።

ያም ሆነ ይህ እንደነ ፍሪድሪሽ ሊስትና ሀይንሪሽ ፔሽ የመሳሰሉትና ሌሎችም ታላላቅ የኢኮኖሚ ፈላሳፋዎች የሚያስተምሩን፣ ኢኮኖሚ ለኢኮኖሚ ተብሎ ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን፣ ዋናው ዓላማው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ ፍላጎት ማሟላት ነው። ስለሆነም በመጀመሪያ መሰረታዊ ነገሮችን፣ ማለትም የተሟላ ምግብ፣ ንጹህ ውሃ፣ መብራትና መቀቀያ፣ መጠለያ ወይም ቤት፣ ህክምናና መሰረታዊ ትምህርት የመሳሰሉት ማሟላት ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የተስተካከሉና ውብ ውብ የሆኑ ከተማዎችን መገንባት ነው። በዚህም መሰረት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያካትትና እንደየደረጃው የሚያሳትፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን ቀስ በቀስ አንድ አገር እያደገ ይሄዳል፤ እንዲሁም ሰፊው ህዝብም ተጠቃሚ ይሆናል። የወያኔ ፖሊሲና የፖሊሲው አውጭዎች በአንፃሩ ይህንን ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረተ-ሃስብ የሚፃረሩ ናቸው።  አንድ አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳይገነባ ህዝብን የሚያሳስቱና ሀብትን የሚያባክኑ ናቸው። በዚያው መጠንም ድህነትን የሚያስፋፉ ናቸው።

ባጭሩ የወያኔ የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ ጥቂቶችን ያደለበ፣ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን ህዝብ ደግሞ ያደኸየ ነው። በየከተማዎች ውስጥ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች(Slums)እንዲፈለፈሉ ያደረገ ነው። ራሱን የሳተ አዲስ የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈለፈል በማድረግ የህብረተሰብን ህግና እሴትን ያናጋ ነው። አገሪቱን መቀመቅ ውስጥ የከተተና አጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ የፈጠረ አደገኛ የኢኮኖሚ ፖሊስ ነው። የማህበራዊ፣ የጤናና ሌሎች ፖሊሲዎችም የኢኮኖሚው ፖሊሲና አካሄድ ነፀብራቆች በመሆናቸውና በግልጽም የሚታዩ ስለሆኑ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይደለም።

ያም ሆነ ይህ የአንድ አገር ዋና መሰረት በሳይንስና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ፣ አጠቃላይ ሀብት ሊፈጥር የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ ነው። የብሄራዊ ሀብት ዋናው መሰረት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ የማኑፋክቱር አብዮት ማካሄድ ነው። የወያኔ የእኮኖሚ ግን በአበባና በጨአት ተከላ፣ በሸንኮራ አገዳና በቡና ተከላ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግን መጣሱ ብቻ ሳይሆን፣ አንድን ህዝብ ከድህነት የሚያላቅቅ አይደለም። እንደሚታወቀው በእርሻ ላይ የተመረኮዘ ኢኮኖሚ በማኑፋክቱር እስካልተደገፈ ድረስ ምርታማ ከመሆን ይልቅ ወደ ታች የማሽቆልቆል ኃይሉ(Decreasing Returns) ከፍተኛ በመሆኑ ለድህነትና ለአጠቃላይ ኋላ-ቀርነት ዋናው ምክንያት ይሆናል።  ኢኮኖሚ ማንኛውንም ነገር የሚወስን በመሆኑ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የማይችል አገዛዝና ምሁር ደግሞ አገሩን ማዳከሙ ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይል እንዲጠቃ ያደርጋል። ህብረተሰቡ ነዝህላል እንዲሆን ያደርጋል። የስራ ባህል መዳበር አይችልም። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ወደ አልባሌ ቦታዎች እንዲሰማራ በማድረግ አገርን የሚያጋልጥ ይሆናል። በዚህም አማካይነት፣ የዕፅ ሱስ መስፋፋት፣ መጠጥ የመጠጣት ባህል ስር መስደድ፣ የሴተኛ አዳሪ መብዛትና ተፈጥሮአዊ ያልሆኑ የወሲብ ግኑኝነት መስፋፋትና፣ እንዲሁም የህብረተሰቡ መንፈስ እንዲዳከም ማድርግ የኢኮኖሚው ፖሊሲና የጠቅላላው ከሳይንስ ጋር የማይገኛኘው ፖሊሲ ነፀብራቆች ናቸው። ይህንን ዐይነቱን አደገኛ አካሄድ መግታት የሚቻለውና ሳይንሳዊ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ የሚቻለው አገዛዙንና ግብረአበሮቹን በመለማመጥ ሳይሆን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ የትርምስና የድህነት ዋናው ምክንያት የሆነውን አገዛዝ ማስወገድ ሲቻል ብቻ ነው። ከሌባ፣ ከገዳይ፣ አገርን ከሚዘርፍና ከሚያዘርፍ፣ በጠቅላላው የአገሪቱን ደህንነት አናግቶ ህብረተሰቡን አቅመ-ቢስ ካደረገ ኃይል ጋር ተቀምጦ መደራደር አይቻልም። መለማመጥም የሚያስፈልግ አይደለም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም። ፀረ-ሳይንስ፣ ፀረ-ፍልስፍና፣ ፀረ-የሰው ልጅና ፀረ ህብረተሰብ አካሄድ ነው። ስልጣን ላይ ቁጥጥ ለማለት የሚፈልግ ካልሆነ በስተቀር የአገራችንን ሁኔታ በጤናማ መንፈሱ ወይም ጭንቅላቱ የሚያይና የሚከታተል፣ አገዛዙ ውስጥም የተማሩ ስዎች ወይም ፖለቲከኞች አለ ሊለን አይችልም። እንደዚህ ብሎ መናገር ኢትዮጵያ ሆይ ዘለዓለሙን ደሃ ሆነሽ ቅሪ፣ ህዝብሽም እየታሸ መኖር አለበት የሚል ብቻ ነው። ከዚህ በመነሳት ደግሞ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ፖለቲካውንና አካሄዱን እንመርምር።

የተቃዋሚው ፖለቲካ በፖለቲካ ሳይንስ መነፅር ሲገመገም !!

በመጀመሪያ ደረጃ  መቃወም ማለት ምን ማለት ነው። ከአንድ ሁኔታ ጋር ወይም ሃሳብ ጋር አለመስማማት ማለት ነው። በእርግጥ የመቃወም ደረጃዎች አሉ። ሙሉ በሙሉ አለመስማማትና ወይም ደግሞ በከፊል መቃወምና በጋራ በሚያሰሩ ነገሮች ላይ አብረው እየሰሩ ሌላውን በሄደት ማስተካከል ወይም መፍታት። ስለ ተቃውሞ ወይንም ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ፖለቲካ በምናወራበት ጊዜ መነሳት ያለብን ስልጣን ላይ ከመውጣት አንፃር ሳይሆን ከአንድ አገርና ከህዝብ ፍላጎትና ምኞት አንፃር ነው መመርመር ያለብን።

በአገራችን በአጭሩ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት የተሰሩና የሚሰሩ ግዙፍ ስህተቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ተቃዋሚ ፓርቲ ነኝ የሚለው የሚነሳው ስልጣን ላይ ከመውጣት አንፃር ብቻ ነው። ከዚህም በመነሳት የፖለቲካ ክፍሉ ጠቧል ሲል ጠቅላላውን የአገራችንን ዕድልና የህዝባችንን አኗኗር ሁኔታ በመመልከት አንፃር ሳይሆን ከራሱ ሁኔታ በመነሳት ብቻ ነው። በሁለተኛው ደረጃ የሚሰራው ስህተት፣ በአገራችን የሚካሄደውን የተቃውሞ ፖለቲካና በስልጣን ላይ መሳተፍ ከካፒታሊስት አገሮች የመደብለ-ፓርቲዎች ሁኔታ ጋር በማነፀፃር ነው። እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ስህተቶችና በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይንሳዊና ፍልስፍናው መሰረት ምን እንደሆነ አለመታወቁ በአጠቃላይ ሲታይ የትግሉን መንፈስ አዳክሞታል። በዚያውም  መጠን አገዛዙ በአረመኔያዊና አገርን በማተረማመስ ተግባሩ እንዲገፋበት አመቺ ሁኔታ ፈጥሮለታል።

በመጀመሪያ ደረጃ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት አገዛዙ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በማካሄድ ህብረተሰቡን አቅመ-ቢስ ባደረገበት ሁኔታና በህዝባችን ላይ አጠቃላይ ጦርነት በማወጅ ህዝብን በሚጨፈጭፍበትና ካለምንም ምክንያት ዜጎችን ወደ እስርቤት ውስጥ በሚወረውርበት ጊዜ ጤናማና አገዛዙን የሚያለሳልስ ወይም እንደራደር የሚያስብል ፖለቲካ ማካሄድ በፍጹም አይቻልም። እንደዚህ ዐይነቱ አካሄድ እጅግ አደገኛ ብቻ ስይሆን አንድን አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳይገነባ ማደርጉ ብቻ ሳይሆን፣ በተዘዋዋሪ አገዛዙ በከፋፍለህ ግዛና ህዝቡን በማታረመስ ፖለቲካው እንዲገፋበት ማበረታታት ነው። ችግሩ የተወሳሰበና ለረጅም ጊዜ እየተሳሰረ የመጣ ቢሆንም፣ አገዛዙ የህብረተስብን ህግና የህብረ-ብሄርን መሰረተ-ሃሳብ የሚፃረር ፖለቲካ የሚያካሄድ በመሆኑ ይህ ዐይነቱ አካሄድ የአንድን አገር ህልውና ያናጋና የሚያናጋ ነው። ይህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን መጪውም ተከታታይ ትውልድ ጤናማ አገርና ህብረተሰብ እንዳይመሰርት ብዙ መሰናክሎችን የተከለ ነው። ከዚህ አንፃር ስንነሳ በአገራችን ምድር አገዛዙን የሚያለማምጥ ፖለቲካ ወይም በመግባባትና በመቻቻል የሚፈታ ፖለቲካ ማካሄድ አይቻልም። አገዛዙ እኔ የማድረገውን አገርን  የሚበታትን፣ ህዝብን የሚያዳክምክና ሀብትን የሚያዘርፍ ፖለቲካ ተቀበሉና እንደኔ አስረሽ ምችው በሉ ነው የሚለው። ባጭሩ አገራችን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የለባትም፤ ህዝባችንም የሰለጠነ ኑሮ መኖር የለበትም ነው የሚለው። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥና ችኮነት እንዴት አድርጎ የተቃውሚ ፖለቲካ ማካሄድ ይቻላል። እንዴትስ በመርጫ መካፈል ይቻላል። ሌላው ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ነን የሚሉት ስህተት የኢትዮጵያን ሁኔታ ለማወዳደር የሚፈልጉት ከካፒታሊስት አገሮች የመደብለ ፓርቲ ሁኔታ ጋር ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ በአውሮፓ ውስጥ፣ በተለይም በምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች የመደብለ ፓርቲዎች ከመፈጠራቸው በፊት አገሮች በመርከንታሊስት የኢኮኖሚ ፖሊስ(Mercantlist Economic Policy)አማካይነት የውስጥ ኢኮኖሚያቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ነበረባቸው። ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባትና ማስተካከል ነበረባቸው። እያንዳንዱ መንደርና ከተማም ርስበርሱ እንዲያያዝ መንገዶችና የካናል ሲሰተሞች፣ በኋላ ደግሞ የባቡር ሃዲዶች መዘርጋት ነበረባቸው። በዚህ አማካይት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ሰው መንቀሳቀሱ ብቻ ሳይሆን በየቦታው አነስተኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣ በኋላ ደግሞ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በመትከል ሰፋ ያለ የስራ ክፍፍልና  የአገር ውስጥ የውስጥ ገበያ(Home Market)ይገነባ ነበር። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ወደ ውስጥ ቀሰ በቀስ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀሱና ማሳደጉ ብቻ ሳይሆን ለምሁራዊ እንቅስቃሴም በር በመክፈት የኋላ ኋላ ለመደብለ ፓርቲዎች መፈጠር አመቺ ሁኔታ ሊፈጥር ችሏል። በካፒታሊስ አገሮች ውስጥ በተለይም ሳይንሳዊ ምርምርና በዚህ አማካይነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ንጥረ-ነገሮች ማግኘትና ማዋሃድና በዚያውም መጠን አዳዲስ ምርቶች ሲመረቱ ይህ ዐይነቱ የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ማሟላቱ ብቻ ሳይሆን የተወሰነውንም የህብረተሰብ ክፍል ምሁራዊ ኃይል ከፍ እንዲል ለማድረግ ችሏል። በዚህ መሰረት የመደብለ ፓርቲ ሁኔታ አስፈላጊና ፓርቲዎችም እንደ አሸን እየፈለቁ መጡ። በአነሳሳቸውም የአንድን አገር ደህንነት ጥቅም እንጥብቃለን ከሚለው አንፃር በመነሳት ሳይሆን፣ የዚህን ወይም የዚያኛውን መደብና የህብረተሰብ ክፍል በኋላ ደግሞ የአካባቢን ሁኔታ አስመልክቶ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለመከላከል የተመሰረቱ ፓርቲዎች ናቸው። በየአገሮች ውስጥ ጠንካራ መሰረት በመጣሉ የአገር አንድነት መጠበቅ አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ ምንም የሚያከራክራቸው ነገር የለም። አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮችም ድንበር አልፈው የደካማ አገሮችን ሀብት የሚቆጣጠሩና የሚዘርፉ በመሆናቸው ከውስጥ አንድነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥለው ከውጭ ደግሞ ብሄራዊ ነፃነታቸውን የሚቀናቀናቸው ኃይል በፍጹም የለም። በዚህም መሰረት የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፖርቲ፣ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ የሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ የግራ ወይም የኮሙኒስትና የግሪን ፓርቲዎች በመባል መቋቋም ቻሉ። የእነዚህ ፓርቲዎች ዋና ዓላማም እንደሚከተሉት ርዕዮተ-ዓለም ስርዓቱን ለመቀየር ሳይሆን እነሱ በሚመስላቸው መንገድ ሁኔታዎችን ለዚህ ወይም ለዚያኛው የህብረተሰብ ክፍል ማሻሻል ነው። በተለይም የሚያነሷቸው ጥያቄዎች የማህበራዊ፣ የቀረጥና የትምህርት ጥራትና የታዳጊ ልጆችን ጉዳይ ነው። ሌሎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በተለይም ሰፊው ህዝብ በሚያገኘው ዝቅተኛ ገቢ ቤት ተከራይቶ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ… ወዘተ. እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች የሚነሱና በፓርቲዎች መሀከል እንደልዩነት የሚታዩና የሚያጨቃጭቁ ናቸው። የኋላ ኋላ ግን በስምምነት የሚፈቱ ናቸው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ክላሲካሉ መንገድ ቢሆንም ካለፉት ሰለሳ ዐመታት ጀምሮ በብዙዎች ፓርቲዎች የፖሊሲ አካሄድ ላይ ተመሳሳይ የሆነ አካሄድ መመልከት ይቻላል። አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች የሶሻል ዲሞክራቶችም ሳይቀሩ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ነው የሚያካሂዱት። በተለይም የፋይናንስ ካፒታል አይሎ በወጣበት ጊዜና ማዕከላዊ ባንኮች(Central Banks)በዜሮ ወለድ አማካይነት ገንዘብ እያተሙ ወይም ሰርተፊኬት እየበተኑና ገንዝብ እየሰበሰቡ እንደገና ለንግድ ባንኮች ገንዘብ በሚያበድሩበት ዘመን ተጠቃሚዎቹ የአየር ባየር ንግድ የሚያካሂዱ ናቸው። ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ፖሊሲና ተቀማጭ ሀብቶችን በርካሽ ገንዘብ መግዛትና ከፍተኛ የሆነ የሀብት ሽግሽግ መኖር አባዛኛዎችን ፓርቲዎች አቅመ-ቢስ አድርጓቸዋል። እንደቀድሞው በሶሻልና በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አማካይነት የተዛቡ ሁኔታዎችን ማሻሻል የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ ስርዓቱ ይንቀሳቀሳል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ኃይሉ ክፍ ያለ ነው። ባጭሩ ማለት የሚቻለው መንግስትና የተለያዩ ፓርቲዎች ስርዓቱ የሚቀናቀኑ ሳይሆን የተወሰነ መሻሻል እንዲኖረው በማድረግ የካፒታሊስቶች የበላይነት የሚጠበቅበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠሩ ኃይሎችና አፈ-ቀላጤዎቻቸው በመንግስት መኪና ላይ ጫና ስለሚያደርጉ መንግስታት የኢኮኖሚው ተጎታቾች እንጂ እንደ ቀድሞው በኢኮኖሚው ላይ የማዘዝ ምንም መብት የላቸውም። ይህም ማለት የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በአውቶኖመስ ደረጃ የሚንቀሳቀሱና ለብዙ ሚሊዮን ሰራተኞች የስራ ዕድል የሚሰጥና የመንግስታቱም የገቢ መሰረት ነው። ማለትም በኢኮኖሚውና በመንግስታት፣ እንዲሁም በፓርቲዎች መሀከል መደጋገፍና መስማማት ቢኖርም በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች የምርት ክንዋኔዎችና የተወሰኑ ግልጋለቶች በግለሰብ ኩባንያዎች ተመርተው የሚቀርቡ ናቸው። እንደየአገሩ ሁኔታ እንደ ባቡር መመላለሻ፣ ሀኪም ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ውሃና መብራት በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ወይም ደግሞ መንግስት በአክሲዮን በከፍተኛ ድርሻ የሚካፈልባቸው ናቸው።

ወደ አገራችን ስንመጣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ የማዕከለኛው ዘመን ወይም ከዚያ የባሰ ሁኔታ እንዳለ በገሃድ የሚታይ ጉዳይ ነው። በስርዓት የተገነቡ ከተማዎች የሉም። በደንብ የዳበረ የስራ ክፍፍልም የለም። እዚህና እዚያ የተቋቋሙ አነስተኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሉም። የውስጡ ገበያ እጅግ ደካማ ነው። አሁንም ቢሆን የአገልግሎት መስኩና ከእጅ ወደ አፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች(Subsistence Economy) ናቸው የህዝቡ የግልጋሎትና የምግብ መሰረቶች። አብዛኛው ህዝብ የስራ መስክ የማግኘት ዕድል የለውም። የአገዛዙ የቀረጥ መሰረት እጅግ ደካማ በመሆኑ የሶሻል ፖለቲካ ማካሄድ አይችልም። በራሱ የዕውቀት ማነስና ስግብግብነት የተነሳ አነስተኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በየቦታው እንዲተከሉ የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ የለውም። የእርሻውን ፖሊሲ ስንመለከት እጅግ የተዝረከረከና ሰፊው ህዝብም አስፈላጊውን የምግብ ነገሮች ገዝቶ የመመገብ ኃይል የለውም። በተጨማሪም በየአካባቢዊና በየመንደሮች ውስጥ የሰውን ኃይልና የጥሬ ሀብት ለማንቀሳቀስ የሚችሉ ዘመናዊ ኢንስቲቱሽኖች የሉም።  ህዝቡን፣ በተለይም ሽማግሌዎችንና ወጣቶችን የሚንከባከቡ እንደዚህ ዘመናዊ ኢንስቲቱሽኖች በፍጹም የሉም። በተለይም ምንም ዕርዳታ ማግኘት የማይችሉትን ሽማግሌዎች የሚንከባከብ መዋያ ቦታና እሮሮአቸውን የሚሰማ ኢንስቲቱሽን በአገሪቱ ምድር አንድም ቦታ የለም።  ይህንን ስንመለከትና ሌሎች ፖሊስዎችን ስናካትት በአገራችን ምድር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት ያለበት ጉዳይ እንጂ በፓርቲዎች ውድድርና እሽቅድምድምነት ወይም ደግሞ በስልጣን መካፈል የአገሪቱ የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈቱ በፍጹም አይችሉም። ሊፈቱ የሚችሉት ከዚህ አገዛዝ ባሻገር፣ ብሄራዊ ባህርይ ባለውና  አገር ወዳድ በሆነ ድርጅት ወይም ድርጅቶች አማካይነት ብቻ ነው።  አገራችን እንደ አንድ ጠንካራ ህብረ-ብሄርና ህብረተሰብ መገንባት እንድትችል ሁኔታው ከፓርቲዎች ባሸገር መታየት ያለበትና፣ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ምሁራን የአገሪቱ የተወሳሰቡ ችግሮች እንዴት ደረጃ በደረጃ መፈታት እንዳለባቸው ማጥናትና ሃሳብ ማቅረብ አለባቸው። የአገራችን ጉዳይ ለፓርቲዎች መተው የለበትም። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በተለያዩ የአፍካ አገሮች ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት ራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፋ ላለ ዕድገት መምጣት እንቅፋት እንደሆኑ ነው።

የብዙዎቹ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ችግር አገዛዙ እስከዛሬ ድረስ የሚከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊስ ምንነትና ይዘት አለመረዳት ነው። ሁሉም ፓርቲዎች በገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚችሉ ነው የሚነግሩን። የረሃብንና የድህነት ጉዳይ፣ የቤትና የንጹህ ውሃ እጦትን ጉዳይና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን እንዴት መፈታት እንዳለበቻው በፍጹም አያሳዩንም። በተጨማሪም ርስበሩስ የተሳሰረና ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዴት እንደሚገነቡና ስትራቴጂያቸውም ምን እንደሆነ ሲነግሩን አይታይም። እንደሚታወቀውና ብዙ ኢምፔሪካል ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት የካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚ በገበያ ኢኮኖሚ መርሆች አማካይነት በፍጹም አልተገነባም። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት በልምድና በሙከራ በመንግስት ጣልቃ-ገብነት የተገነቡና እየተፍታቱ የመጡ ኢኮኖሚዎች ናቸው በካፒታሊስት አገሮች መፈጠር የቻሉት። አብዛኛዎቻችን የካፒታሊዝምን ዕድገት በተሳሳተ መልክ ስለምናነብና የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስም ስላሳሳተን ለአገራችንም የሚበጀው የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ ነው ብለን ደምድመን ተቀምጠናል። ልክ እንድ አሜሪካ አገር የሪፓብሊካን ፓርቲ በመንግስትና በግል ተነሳሽነት የተቀነባበረና የተጠና ወይም የታቀደ የኢኮኖሚ ክንዋኔና በመንግስት የሚደጎም የግልጋሎት መስጫ መስክን ከሶሻሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር እያምታታን በማቅረብ ወጣቱን ማሳሳታችን ብቻ ሳይሆን ጤናማና ሳይንሳዊ ውይይት እንዳይካሄድ መንገዱን ሁሉ ዘግተናል። በተለይም በቅርቡ በቪዥን ኢትዮጵያ እንደ አማራጭ ሆኖ የቀረበው የንጹህ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ  የካፒታሊዝምን ኢኮኖሚ አፀናነስና አመሰራረት፣ እንዲሁም እያደገ መምጣትና ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሆን ዓለም አቀፋዊ ባህርይንም መያዝ በቅጡ ካለመረዳትና ካለመጥናት የተነሳ ነው። ካፒታሊዝም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንውን የሚካሄድበት የተወሳሰበ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ሲሆን፣ የኢኮኖሚውን ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች የያዙት ኦሊጎሎፖሊስቶች በመባል የሚታወቁ ትላልቅ ኩባንያዎች ናቸው።

የአብዛኛዎቹ የዚህን ወይም የዚያኛውን ፓርቲ ስም የያዙ የተቃዋሚ ድርጅቶች ሌላው ዋና ችግር የረጅም ጊዜ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውጤቶች አይደሉም። የአውሮፓን ፓርቲዎች አመሰራረት ታሪክ ስንመለከት ህብረተሰቡ ከመፍታታቱ፣ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የስራ ክፍፍል ከመዳበሩ በፊት፣ ከተማዎች በየቦታው ከመገንባታቸውና ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከመዳበሩ በፊት ፓርቲዎች በፍጹም አልተወለዱም። የጊዜውም ሁኔታ የሚፈቅድ አልነበረም። በአገራችንና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለው ችግር ሰፋ ያለና የጠለቀ ምሁራዊ ውይይትና ክርክር፣ እንዲሁም እያንዳንዱ አገር ያለበትን የማቴሪያልና የህዝቡን ንቃተ-ህሊና ሁኔታ በደንብ ሳይገመገሙ ፓርቲዎች ስለሚቋቋሙ ይህ ሁኔታ በራሱ ዕድገትን የሚቀናቀን ይሆናል። የፓርቲ መሪዎች የማያስፈልግ የበላይነትን በመመስረትና ከውጭው ኃይል ጋር በመተሳሰርና የማይሆን ምክር በመቀበል እነሱ ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽል ምንም ዐይነት መሰረታዊ ለውጥ አያመጡም። እንዲያውም ራሳቸው አዲስ የገዢ መደብ በመሆንና ራሳቸውን በማደለብ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ያስፋፋሉ።  ባለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለው ችግር ይህ ነው። ወደ አገራችንም ስንመጣ ከተማሪው እንቅስቃሴ ትምህርት ቀስሞ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለማዳበር፣ ንቃተ-ህሊናን ለማሳደግና ታሪካዊ ኃላፊነትን ለመቀበል ከመዘጋጀት ይልቅ አርባ ያህል ዐመታት ዝም ብሎ ባከነ፤ ተተኛ። አብዛኛዎቹ የመሰላቸው የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር በመደብለ-ፓርቲ፣ በህገ-መንግስትና በምርጫ ብቻ ማሻሻል ወይም መለወጥ የሚችሉ መስሎ ስለታያቸው ደጋግመው የሚያነሱት ይህንን ብቻ ነው። የአገራችንን መሰረታዊ ችግሮች ለመረዳትና ምክንያቱን ለመፈለግ ወደ ኋላ በመሄድ ለመመርመር አይቃጡም። የራሳቸውንም የመንፈስ ሁኔታና ድርጊታቸውንም ለመመርመር ፍላጎትና ቆራጥነት ስለሌላቸው መስራት ይገባቸው የነበሩ ፍልስፍናዊ፣ የቲዎሪና የሳይንስ ምሁራዊ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ አልቻሉም። ምርምርና ጥናት ሲያደርጉና፣ ታዳጊውን ትውልድና ህዝብን ሲያስተምሩ አይታይም። በምድር ላይ የሚታየውንም የተዝረከረከ ሁኔታ፣ የስራ አጥነት መብዛት፣ የወጣቱ መንቀዋለልና የአልባሌ ነገሮች ሰለባ መሆን፣  የኑሮ ውድነትና አጠቃላዩ የሰፊው ህዝብ የኑሮ ሁኔታ፣ የምግብ፣ የንጹህ ውሃና የቤት ጉዳይን እያነሱ እነዚህ ነገሮች እንዴት ሊቀረፉ እንደሚችሉና፣ በአጠቃላይ ሲታይ አገራችን በጠንካራና በተስተካከለ መሰረት ላይ እንድተገነባ የሚያስችል ሃሳብ ሲዘነዝሩ በፍጹም አይታዩም።

ለማንኛውም የዛሬው አገዛዝ የግዴታ መወገድ ያለበት ቢሆንም፣ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ከማምራታቸው ወይም እሽቅድምድሞሽ ከማድረጋቸው በፊት ብዙ የቤት ስራዎችን መስራት አለባቸው። ይህም ሆኖ የአገራችን አጠቃላዩንና የተወሳሰበ ሁኔታ ለሚቀጥሉት ሰላሳና አርባ ዐመታት በመደብለ-ፓርቲዎችና በምርጫ አማካይነት የሚፈታ ሳይሆን በጋራ ግንባር አማካይነት ብቻ ነው። በዚህ ዐይነቱ የጋራ ግንባር በየስምንት ወይም በየአራት ዐመቱ ጠቅላይ ምኒስተሮችና ሌሎችም በመፈራርቅ የግዴታ አገር መገንባት መቻል አለባቸው። በተለይም ደግሞ አገር በፀና መሰረት ላይ ሊያስገነባ የሚችል ሳይንሳዊና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል አለባቸው። ይህም ማለት ከውጭ ግፊት መላቀቅ አለባቸው። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን አሽቀንጥረው መጣል አለባቸው። በዚህ አማካይነት ብቻ ቀስ በቀስና በልምድና በተመክሮ ጠንካራና ለሰፊው ህዝብ አለኝታ የሚሆን ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል። ስለሆነም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ነን የሚሉ ሁሉ የራሳቸውን ሁኔታና ሚና መመርመር የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። አገራችን ብዙ ንትርክን አትፈልግም። ህዝባችንም ምኞቱንና ህልሙን ተግባራዊ የሚያደርግለትን ህብረተሰብአዊ ኃይል ይፈልጋል እንጂ በላዩ ላይ ቅጥጥ ብለው እንደገና ለሌላ ስቃይ የሚዳርጉትን ኃይሎች በፍጹም አይሻም።

ምሁራናዊነትን በፖለቲካ ሳይንስ መነፅር የመመልከቱ አስፈላጊነት !

በመጀመሪያ ምሁር ማለት የተማረ ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ብሎ አንድን ነገር ከሁሉም አቅጣጫ መመልከት የሚችል ማለት ነው። በሌላ ወገን ማንኛውም የአካዳሚ ትምህርትን የቀሰመ ምሁራዊ ባህርይ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። ያም ሆነ ይህ አንድ ሰው ትምህርት ቤት የሚሄደው ዕውቀትን ለመቅሰም ነው። የተሻለ ዕውቀት በማግኘት ራሱንና የተፍጥሮን ህግጋት ብቻ ሳይሆን አንድ ህብረተሰብም በምን በምን ህጎች እንደሚገዛ በማወቅ ምን ምን እርምጃዎች ቢወሰዱ ሚዛናዊ የሆነ ዕድገት ሊመጣ ይችላል ብሎ መጠየቅ እንዲችል ነው የሚማረው። ከዚያም በመነሳት ላልተማረው ዕውቀቱን ማካፈሉ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ወይም ደግሞ የጠቅላላውን ህብረተሰብ ሁኔታ ለመለወጥና ለማሻሻል የሚችል መሆን አለበት። ከዚህ ስንነሳ መማር ወይም ምሁር መሆን ዲስፕሊናዊ ስርዓትን የሚያካትት፣ ስነምግባርንና ግብረ-ገብነትን የሚያጠቃልልና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ከራሱ ወይም ከደሙ ጋር በማዋሃድ ኃላፊነትን መወጣት ማለት ነው። በአጭሩ አንድ ምሁር ወይም ምሁሮች የስልጣኔ ዘርጊዎች፣ የህዝብና የአገር አልኝታዎች መሆን አለባቸው። ታላቁ ሺለር እንደሚለው መማር ማለት ዳቦ ለማግኘት ሳይሆን አንድን ህዝብ ከጨለማ በማውጣት የስልጣኔ ብርሃንን ማንጸባሪቂያ መሳሪያ ነው። ስለሆነም የምሁሮች ዋና ተግባር አንድ ህዝብ ያለውን የተደበቀ የመንፈስ ኃይል በማውጣት ታሪክን እንዲሰራ ሊያደርግ የሚያስችለውን መንገድ ማሳየት ነው። ጠቅላላው ህዝብ መንፈሱን ማደስ እንዲችልና፣ እያንዳንዱ ግለሰብም ማንነቱን በማውቅ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን እንዲወጣ ማድረግ የምሁራን ኃላፊነት ነው። ስለሆነም አንድ ምሁር ሰብአዊነትንና እኩልነትን የሚያስተምርና ራሱም በኑሮው የተቆጠበና ሌላውን አልተማረ የሚባለውን የማይንቅ መሆን አለበት።  የመማር ወይም ምሁር የመሆን ትርጉሙ ይህንን መምሰል አለበት። ስለሆነም ነው በጥንት ዘመን ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ እስከ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ የተማሩ ምሁራን የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የህግ፣ የሶስዮሎጂና የጥበብ አፍላቂዎች በመሆን በአውሮፓ ምድር ውስጥ ስልጣኔን ማምጣት የተቻሉት። እኛም የዚህ ዕውቀት ተጠቃሚዎች መሆን የቻልነው የግሪክና የአውሮፓ ፈላስፋዎች መሰረት በመጣላቸው ነው። በአውሮፓ ምድርና አሜሪካን ድረስ መጥተን መማር የቻልነው እነሱ ባፈለቁት ቴክኖሎጂዎች ነው። በአህያና በፈረስ ተጉዘን በመምጣት ሳይሆን በአውሮፕላን በረን ነው እዚህ መጥተን ለመማር፣ ለመስራትና ቤተሰብ ለመመስረት ዕድል ያገኘነው።

ከላይ ስንነሳ ከአንድ የተማረ ሰው የሚጠበቀው ሃቀኝነትን ነው። ለዕውነት መቆምን ነው። ለስልጣኔ ታጥቆ መነሳትን ነው። የተማረ ኃይል ወይም ምሁር የአንድ አገር ህዝብ አለኝታ እንደመሆኑ መጠን ማስቀደም ያለበት የህዝቡን ፍላጎት እንዴት ማሟላት አለብኝ? ምን ምን ዐይነት ፖሊሲዎች ብከተል ዕድገትን አመጣለሁ ? ብሎ የሚያወጣ የሚያወርድ እንጂ ለዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖች በማጎብደድ ራሱንና አገሩን የሚሸጥ አይደለም። ስለሆነም አንድ የተማረ ኃይል ወይም ምሁር በምንም ዐይነት የራስን ጥቅም በማስቀደም አንድ ህዝብ በደል እንዲደርስበት ማድረግ የለበትም። አንድ የተማረ ሰው በአገሩ ውስጥ ኃላፊነት ከተሰጠው በመጀመሪያ ደረጃ የራሱን ጥቅም ማስጠበቅና ለውጭ ኃይሎች ጠበቃ መቆም ሳይሆን የህዝብንና የአገርን ጥቅም ማስጠበቅ ነው። ህዝቡና አገሩ እንዲከበሩ የተቻለውን ማድረግና፣ የአገሩን ዕድገት የሚቀናቀንን ደግሞ በተቻለው መንገድ መዋጋት የሚችል መሆን አለበት። ይህንን የማያደርግ ወይም ለስልጣኔ ጠበቃ የማይቆምና አገሩ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ጠንካራ አገር እንድትሆን የማይጥር እንደዚህ ዐይነቱ እንደምሁር ሊቆጠር በፍጹም አይችልም።

ያለፉትን የሃምሳ ዐመታት የአገራችንን የምሁር ታሪክ ስንመረምር፣ አገራችን እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ልተደርስ የቻለችው አገር፣ ህዝብ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ግለሰብአዊ  ነፃነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ህብረተሰብና ብሄራዊ ነፃነት፣ እንዲሁም ህብረ-ብሄር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያልገባው ምሁርና የቢሮክራሲያዊና የቴክኖክራቲክ ትውልድ እንደ አሸን በመፍለቃቸው ነው። አገራችን ባለፉት አርባ ዐመታት ፍዳዋን ያየችው በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን፣ ፊደል በቆጠረው አማካይነት ነው። ይህንን የሚክድ ካለ በአገራችን ታሪክ ውስጥ ምን ምን በደል እንደተፈጸመ ያልተከታተለ ብቻ ነው። ይህ ሲባል ግን ለአገሩ የሚያስብና ቆርጦ በመነሳት አገሩን የስልጣኔ ባለቤት ለማድረግ የተፍጨረጨረ አልነበረም ማለት አይደለም። ይህ ኃይል ግን በጣም በጣት የሚቆጠር ነው።

ለመሆኑ ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ።  በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ የምሁር ድክመት ሊደርስ የቻለው በአንድ በኩል በህብረተሰብአችን አስቸጋሪ አወቃቀርና፣ በተለይም ባለፈው 60 ዐመት በገዢ መደቦች በተሰራ ስህተት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በራሱ በአጠቃላይ አነጋገር በምሁሩ ስህተት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በየኢፖኩ ስልጣንን የጨበጡ አገዛዞችና የቢሮክራሲው ኃይል ለስልጣኔ የሚያመቸውን፣ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥር የሚያስችለውን፣ አዳዲስ የነቁ የህብረተሰብ ኃይሎች እንዲፈጠሩ አመቺ የሚሆነውን ዕውቀት ፈልገው ተግባራዊ የማድረግ ኃይልና ብቃት አልነበራቸውም። በተጨማሪም የምዕራብ አውሮፓና ሌሎች ኋላ በዕድገት የመነጠቁ አገሮች እንዴት ሊሻሻሉ ቻሉ? ምን ምን እርምጃዎችን ቢወስዱ ነው እዚህ ዐይነቱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ በመድረስ የህዝባቸው ኑሮ እንዲሻሻል ማድረግ የቻሉት ? ብለው የመጠየቅ ፍላጎትና ብቃት አልነበራቸውም። በእነሱ አስተሳሰብ አንድ አገር በትንሽ ነገር ብቻ እንደ ሀገር የሚቆይ የሚመስላቸው እንጂ በየጊዜው በቁጥር እያደገ ከሚመጣ ህዝብ ጋር የሚመጣጠን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት ህዝቡን ማስተናገድ እንደሚገባና ለዚህ ደግሞ ታሪካዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንደነበረባቸው የተገነዘቡ አልነበሩም። ባጭሩ ያልተገለጸላቸውና፣ በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ ነበሩ።  የአንድ ህዝብና የታዳጊው ትውልድ ዕጣ ምን መሆን እንደሚችል ስለማይታሰብና፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው የቢሮክራሲውና የቴክኖክራት ትውልድም ጉዳያቸው ስላልነበር አገራችንን መቀመቅ ውስጥ ሊከቷት ችለዋል። ጭቅጭቅ  ውስጥ እንዳንገባ ይህንን ጉዳይ ካደጉ የካፒታሊስት አገሮችና ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ ጋር ማወዳደር ያስፈልጋል።

በአውሮፖ ታሪክ ውስጥ የትምህርትን አሰጣጥ ታሪክ ስንመለከት ልጆችን ከልጅነታቸው ጀምሮ የመኮትኮቻ ዘዴዎች ነበሩ። ይህ ዐይነቱ ጭንቅላትን የመኮትኮቻ ዘዴ ቀደም ብሎ ጭንቅላትን መኮትኮቻ ዘዴ(Early Childhood Education System) በመባል ይታወቃል። እነዚህም ጂምናስቲክ፣ ሙዚቃ፣ ሰዋስውና ቋንቋ፣ ጂኦሜትሪና የአነጋገር ስልት(Rhetoric) ናቸው። እንደዚህ ዐይነቱ የትምህርት አሰጠጣና ታዳጊውን ትውልድ በረቀቀ መልክ እንዲያስብ የሚያደርገው ትምህርት በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው በግሪክ በ5ኛው ክፍለ-ዘመን ተግባራዊ የሆነና ለፈላስፋዎች፣  ለሳይንስ ተመራማሪዎች፣  ለማቲማቲክስና ለልዩ ልዩ ለሰው ልጅ ለሚጠቅሙ ዕውቀቶች  መፍለቅ በር የከፈተ ነው። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት ነው የኋላ ኋላ ሬናሳንስ ለሚባለው የአውሮፓው የስልጣኔ መሰረት ለሆነው መንገድ መቀየሻ ለመሆን የበቃው። ይህ ዐይነቱ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በጀርመን ምድር በታላቁ ዊልሄልም ሁምቦልድት ረቆ በመውጣት ለጀርመን ዕድገት አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ነው። ስለሆነም ጀርመን የገጣሚዎችና የአሳቢዎች አገር ተብሎ መጠራቱ ብቻ ሳይሆን በ20ኛው ክፍል ዘመን ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው የኖብል ሽልማት ተሸላሚ ከጀርመን አገር ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቆ የወጣና ሳይንሳዊና ቴክሎጂያዊ ግኝቶችን ዕውን ያደረገ ነው። ይህ የመማሪያ ዘዴ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በመስፋፋቱ በየቦታው የማሰብ ኃይሉ ከፍ ያለና በሁሉም አቅጣጫ ሊያስብ የሚችል ኃይል ብቅ ማለት ቻለ። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ግኝቶች ብቻ ሳይሆን በከተማ ግንባታዎችና በህንፃ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ የሰውን ልጅ የአኗኗር ዘዴ በፍጹም ቀየረው። አንድ ውጥ የሆኑ የህንፃ ስራዎች ብቻ ሳይሆኑ ልዩ ልዩ የህንፃ አሰራር ስልቶች በመዳበርና በመፍልቅ በራሳቸው ለፈጠራ ስራ የሚያመቹ ሆኑ። በዚህም አማካይነት ጥበባዊና ህብረተሰብአዊ በማድረግ ግለሰቦች ፈጣሪዎችና ራሳቸውን እንዲችሉ ተደረጉ።

በተለይም በ15ኛው ከፍል-ዘመን በማርቲን ሉተር የታወጀው እያንዳንዱ ግለሰብ የህሊናው ተገዢ መሆኑን እንዲረዳ ማድረጉና ቀደም ብለው የሃይማኖት ትምህርት ብቻ ይሰጥባቸው የነበሩ ገዳማት ህዝቡን ለማስተማር መለወጣቸው ይህ ዐይነቱ ሰፊውን ህዝብ የማስተማሩና የማንቃቱ ዘዴ ተኝቶ የነበረውን የጀርመንና የኋላ ኋላ ደግሞ የተቀረውን የአውሮፓ ህዝብ እንዲነቃና በራሱ ላይ እንዲተማመን ማድረግ ቻለ። ስለሆነም በፕሮቴስታንት እሴት ላይ የተመሰረተው የትምህርት አሰጣጥ ልዩ ዐይነት ስነ-ምግባርንና የስራ ባህልን በማስፋፋት በራሱ ለካፒታሊዝም ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ ችሏል። በጊዜው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በተስፋፋባቸው ቦታዎች በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ፕሮቴስታንት ሃይማኖትነት የተቀየረ የማማር ዕድል በማግኘቱ በዚያ አካባቢ የስራ ባህል መዳበርና የኢኮኖሚ ዕድገት ምጥቀት መታየት ቻለ። እንደ እንግሊዝ ባሉ አገሮች ደግሞ ከሌሎች ጋር በመሆን ለኢንዱስትሪ አብዮትና ለቴክኖሎጂያዊ ለውጥ መሰረት መጣል ተቻለ። በአጠቃላይ ሲታይ የፕሮቴስታን ሃይማኖት በተስፋፋባቸው አገሮች በተለይም በስካንዲኔቪያን አካባቢዎች ልዩ ዐይነት የስራ ባህልና ከሙስና የፀዳ ፖለቲካዊ አስተዳደር መዳበር እንደቻለ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። በአጭሩ ትክክለኛ ዕውቀት ራስን ለማወቅ፣ ኃላፊነትን ለመቀበልና፣ የህብረተሰብአዊና ህጋዊ ተገዢ መሆን፣ ስራን በዲሲፕሊን መስራትና ኃላፊነትን መወጣት፣ የመፍጠር ችሎታን ማዳበርና ጠቅላላው ህብረተሰብ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ ሊያያዙ የሚችሉት መሰረታዊ ከሆነ የትምህርት አሰጣጥ ለውጥ ጋር ነው።

ወደ እኛና ወደ ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ስንመጣ  ከ1950ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የገባውና ተግባራዊ የሆነው የትምህርት ዐይነት ላይ በተጠቀሰው መልክ ባለመሆኑ ተማሪውን አርቆ አሳቢ፣ ፈጣሪና ታታሪ፣ እንዲሁም በዲሲፕሊን የሚገዛ አላደረገውም። እየተሸመደደ አንድ አንድ የሚገኝበት ትምህርት ከተግባር ጋር ባለመያያዙ በየአገሮች ውስጥ ዝርክርክነትን ከማስፋፋቱ በስተቀር አዲስ የሆነ ዕምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ አይደለም። በዚህም ምክንያት በየአገሮች ውስጥ ብሄራዊ ስሜቱ የዳበረ፣ ለህሊናው የሚገዛና፣ በሁሉም አቅጣጫ በማሰብ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን በመውሰድ የየአገሩን ህዝብ ፍላጎት ተግባራዊ ሊያደረግ የሚችል ኃይል ሊፈጠር አልቻለም። በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተግባራዊ የሆነው ትምህርት በራስ ላይ ዕምነት እንዲያድር ከማድረግ ይልቅ ለውጭ ኃይሎች የሚያጎበድድና ራሱ ተሸማቆ ሰፊውም ህዝብ እንዲሸማቀቅ ለማድረግ የበቃ ነው። በተለይም ዘመናዊነት የሚባለው(Modernization) በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ያልተመሰረተ የምርት አመራረት ዘዴና የፍጆታ አጠቃቀም ከ1950ዎቹ ጀምሮ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና በአገራችንም ምድር በመስፋፋቱ ብሄራዊ ስሜት ያለውና ህዝብን የሚወድ ህብረተሰብአዊ ኃይል ብቅ እንዳይል ለማገድ በቃ። የዘመናዊነት ዋናው ዓላማም በጊዜው በየአገሮች ውስጥ  በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የተስተካከለ ዕድገት ማምጣት ሳይሆን፣ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የፍጆታ ተጠቃሚ ማድረግ ነው። በዚህም መሰረት በአንድ አገር ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣና ብሄራዊ ስሜቱ ያደገ የህብረተሰብ ኃይል እንዳይፈጠር ማድረግ ነው። የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሳይንስና የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ከመሆን ይልቅ የጥሬ ሀብት አምራቾች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ በኢኮኖሚስቶች የተጠና ማሳሳቻ መንገድ ነው።

ከዚህ አጭር ትንተና ስንነሳ የአገራችን ኋላ መቅረት ዋናው ምክንያት በእንደዚህ ዐይነቱ የተበላሸ የትምህርት ዘዴ ምክንያት የተነሳ በመሆኑ፣ ከሁለተኛ ደረጃና ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው የወጡ የአካዴሚክስ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የአገርና የህዝብ አለኝታ ሊሆኑ በፍጹም አልቻሉም። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና ሰዎችም ሊሆኑ አልበቁም። አንዳንዶችም በአስተሳሰባቸው ውስን ስለነበሩ ዕድገትንና ስልጣኔን የመግታት ኃይላቸው ከፍ ያለ ነበር። በተለይም በቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰጉትና ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች የነበራቸው ግለሰቦች ከአገራቸው ይልቅ የውጭ ኃይል ተገዢዎች እንጂ ብሄራዊ ተልዕኮ እንዳላቸው ለመረዳት የሚችሉና የህዝብ አገልጋይ መሆናቸውን የተገነዘቡ አልነበሩም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች በብሄረሰብ የተከፋፈለችና፣ የህብረ-ብሄር አወቃቀርና አገነባብ ባልተጠናቀቀበት አገር ተጨቁነናል ከሚባሉት ብሄረሰቦች ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦችን በመመልመል አለመተማመን እንዲፈጠርና አገር ለመበጥበጥ የሚያመች ሁኔታ መፍጠሩ ለውጭ የስለላ ኃይሎች ቀላል ነበር።  በአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ዘመን በየዋህነት ለአሜሪካና  ለእንግሊዝ ኤምባሲዎች የተሰጠው ትላልቅ የጋሻ መሬት የአገርን ሰላም ለማናጋትና ዕድገትና ሰላም እንዳይመጣና እንዳይሰፍን የውስጥ ኃይሎችን ለመመልመል የሚያመች ነበር። እነዚህ በአሜሪካን የስለላ ድርጅት የተመለመሉ ኢትዮጵያዊ ኃይሎች አገራቸውንና ህዝባቸውን በመካድ ነፃነትን የሚቀዳጁ ስለመሰላቸው በአገራችንና በህዝባችን ላይ ጦርነት አወጁ። ቆሜለታለሁ ያሉትን ህዝብና፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ በማሳሳት ህይወቱ እንዲቀጭ አደረጉ። የተቀረው ደግሞ ህይወቱ ብዥ ብሎበት የመንፈስ ስላም እንዳያገኝ አደረጉት። በዚህ ዐይነቱ ርኩስ ስራ ለብሄረሰቤ ነፃነት እንታገላለን ያሉና ወደ ጫካ የገቡ ብቻ ሳይሆኑ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት የተማሩና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኙ በኋላ በአገሪቱ የስልጣን እርከን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ነበሩ። አንድ ሰው የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኘ በኋላ ወደዚህ ዐይነቱ አገርና ታሪክ አፍራሽ ተግባር መሸጋገሩ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው። ዛሬ ታዲያ እንደነዚህ ኃይሎች የታሪክ ወንጀል እንዳልሰሩ ሁሉ አሁን ደግሞ ቅዱስ በመምሰል በሁለት ወንድማማች ህዝቦች መሀከል ዕርቅ መደረግ አለበት እያሉ ከደሙ ንጹህ ለመምሰል ወጣቱንና የዋሁን ኢትዮጵያዊ ያታልሉታል።

በዚህ ዐይነቱ አገርን አፍራሽነት ተግባር አያሌ ኃይሎች የተሳተፉበት ነው። አንዳንዶቹ ግለሰቦችን በመጥላትና በማኩረፍ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በደንብ የማያውቁትን ርዕዮተ-ዓለም ለመዋጋት ሲሉ በጥላቻ መንፈስ ብቻ በመነሳሳት በህዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት ያወጁና ዛሬ ደግሞ ትላልቅ ሰዎችና የአገር ተቆርቋሪ በመምሰል በየቦታው ለቃለ-መጠይቅ የሚቀርቡና መግለጫም የሚሰጡ ናቸው። የዚህ ሁሉ ችግር ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአንድ ሰው ጭንቅላት እንዲበስልና መጥፎውን ከደጉ ለይቶ ያውቅ ዘንድና ተመራማሪም ይሆን ዘንድ በትክክለኛ ዕውቀት ከልጅነቱ ጀምሮ መኮትኮቱ ብቻ ሳይሆን ራሱም ጥረት ማድረግ እንዳለበት ነው። የጭንቅላትን መብሰልና መዳበር በሚመለከት እነሄገልና ካንት ብቻ ሳይሆኑ በዘመኑ ሳይንስም እነ ጄን ፒያጌት የመሳሰሉት ያጠኑና በኢምፔሪካል ደረጃም ለማረጋገጥ የቻሉ ናቸው። በተለይም በሄገል ጥናት መሰረት ይህ ዐይነቱ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ዕድገት ከማቴሪያላዊ ዕድገት ለውጦች ጋር የተያይዘ ሲሆን፣ አንድ ህብረተሰብ በስራ ክፍፍል እየዳበረና እየተሰበጣጠረ ሲመጣ፣ እንዲሁም ደግሞ ውብ ውብ ከተማዎች ሲገነቡና ህዝቡ በንግድ አማካይነት ርስ በርሱ ሲገናኝ የማሰብ ኃይሉ ማደጉ ብቻ ሳይሆን ወደ ሲቪል ህብረተሰብ እንደሚሸጋገር ነው። ስለሆነም ትክክለኛ ዕውቀት፣ ከተማዎችና መንደሮች በሚገባ መገንባትና ማደግ በአዕምሮ ዕድገትና መዳበር ላይ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ መካድ ወይም አልቀበልም ማለት ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን ዕድገትና ስልጣኔ በአገራችን ምድር ላይ እንዳይመጡ መሰናክል እንደመፍጠር ይቆጠራል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ባለፉት አርባ ዐመታት በአገራችን ምድር የተከሰተው ፖለቲካዊ ውዝግብና የርስ በርስ መገዳደል የራሱን ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል። ከዚህ ዐይነቱ ውዝግብ የተረፈውና ወደ ውጭ ለማምለጥ የቻለው በተለያዩ አገሮች በትምህርትና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመሰመራት ይኖራል። አብዛኛዎቻቸን ከሃያና ከሰላሳ ዐመታት በየአገሩ ተሰበጣጠርን ስለምንኖርና ስለምንሰራ ሳንወድ በግድ በየአገሩ የሰፈነው የአኗኗር ስልት፣ ባህልና ህሊናዊ አወቃቀር እንድንቀበል ተገደናል። በሶስይሎጂ ሶስያላዤሽን የሚሉት ነገር እኛንም አዳርሶታል ማለት ነው። በመሆኑም በየአገሩ የሰፈነው የፖለቲካ ክንዋኔ ሰለባዎች ለመሆን ችለናል። እንደየፖለቲካ ንቃተ-ህሊናችን የየአገሮችን የፖሊቲካ አካሄድ የምንደግፍም የምንቃወምም አለን፤ ካሊያ ደግሞ ከፖለቲካ ዓለም ተገልለን የምንኖር አለን። ያም ሆን ይህ አሜሪካን የሚኖረው ሳይወድ በግድ የአሜሪካንን የአኗኗር ዘዴና(Way of Life) የፖለቲካ ስልትና የሶሻል ስርዓት ትክክል ነው ብሎ የሚቀበል አለ። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሚኖረው ደግሞ እዚህም የካፒታሊስት ስርዓት ቢስፈንም የማህበራዊ አኗኗሩ ከአሜሪካኑ ስለሚለይና የመንግስታትና የፓርቲዎች ፖለቲካ ለየት ያለ በመሆኑ የአውሮፓውን ዕድገት ትክልል ነው ብሎ የሚቀበልና ስሻላይዝድም የሆነ አለ። ከዚህ ስንነሳ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና አህጉሮች የሚኖሩ ሳይወዱ በግድ የየአገሩን የአሰራር ስልትና አስተሳሰብ፣ እንዲሁም የአኗኗር ስልቶች እንዲቀበሉ ተገደዋል። መቀበላቸውም እንደመጥፎ መታየት የለበትም። ችግሩ ግን ሂሳዊ በሆነ መንገድ መታየት ካልተቻለና በቡድን የተደራጀም ሆነ ያልተደራጀ ዕምነቱን ወደ ርዕየተ-ዓለምነት ከለወጠና የአንድ አገር ጠበቃ ከሆነ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም አሜሪካን የሚኖረው በተለይም በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚሳተፈው ኢትዮጵያዊና የግንባር ቀደምትነትን የያዘው የአሜሪካንን ኃያልነት የተቀበለ ሲሆን፣ በአገራችንም ሊካሄድ የሚችለው ፖለቲካ ከአሜሪካ ቁጥጥርና ተፅዕኖ ውጭ ሊሄድ እንደማይችል አምኖ የተቀበለ ይመስላል። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሚኖረውና እንደኔ ያለው የተለየ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ያለው ደግሞ የግዴታ የአንድ አገር ዕድልና የህዝቦችም ህይወት በውጭ ኃይል ሳይሆን በአገሩ ህዝብ መወሰን አለበት ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚታገል ነው። ስለሆነም ይላል፣ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሚኖረው የተወሰነው ኢትዮጵያዊ ኃይል በኢትዮጵያ ምድር ሰላም እንዲሰፍን፣ መረጋጋት እንዲመጣ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው ዕድገት መሰረት ሆነው በአገራችን ምድር የተስተካከለና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆን ከተፈለገና፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና የሰለጠነ የሲቪል ማህበረሰብ እንዲፈጠር ከተፈለገ የግዴታ ከአሜሪካን ኢምፔያሊዝም ቁጥጥርና ተጽዕኖ መላቀቅ አለብን ይላል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የተለየ ሶሻላይዜሽንና የትምህርትና የስራ ልምድ ወደድንም ጠላንም በአገራችን የዕድገትና የፅረ-ዕድገት ሂደት ላይ የራሳቸው ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ማለት ነው። ይህ ጉዳይ ደግሞ ውስጥ ካለውና ጨካኝ ከሆነው ስርዓት ጋር ከሚታገለውና አስቀያሚ ኑሮ እንዲኖር ከተገደደው ወደ መቶ ሚሊዮን ያህል የሚጠጋ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ጋር ያጋጨናል ማለት ነው። ሳንወድ በግድ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ማለት ነው። ከእንደዚህ ዐይነቱ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት የግዴታ የጭንቅላት ትግል ማካሄድና ሚናችንንም ማወቅ አለብን ማለት ነው።  በሌላ ወገን በአገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም ያለውን ሁኔታ ስዳስስ በሁላችንም ዘንድ ያለው የፖለቲካ ግንዛቤ በጣም ደካማና፣  በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ፖለቲካ የሚባለውን ነገር በየዋህነት የምንመለከት ነው የምንመስለው።  መቀበል ያለብን አንድ መሰረታዊ ሀቅ ግን ማንም አገር ለዘለዓለም የበላይነቱን ይዞ መቆየት እንደማይችል ነው። ማንኛውም አገር ከውስጥ ባለው ያልተስተካከለ የሀብት ክፍፍል፣ የማህበራዊ ሁኔታ አለመስተካከልና፣ አገዛዞች የመንግስቱን መኪና የበለጠ ሚሊታራያዝ በማድረግ ወደ አምባገነንነት መሸጋገር፣ እነዚህና ሌሎች አያሌ ነገሮች ማንኛውንም ህብረተሰብ ያናጉታል።

ያም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ ፖለቲካዊ ሂደትና ህዝባዊ መተሳሰርና የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የተማረ ኃይል የሚጫወተው አሉታዊና አዎንታዊ ሚና እንዳለ በኢምፔሪካል ደረጃ የተረጋገጠ ነው። ይህንን በቀላሉ ለመረዳት አውሮፓ አገሮች ያሉበትን ሁኔታ ከኛው ጋር ማወዳደርና ማነፃፀር አለብን። ይህንን የማንቀበል ከሆነ ደግሞ አምላክ እነሱን ሲፈጥራቸው ለየት አድርጎ የፈጠራቸው ናቸው የሚለውን የዘረኝነት ቲዎሪ አምነን እንድንቀበል እንገደዳለን ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ለዘለዓለም ድሆችና ለማኞች፣ እንዲሁም ተሰዳጆች ሆነን እንቀራለን ማለት ነው።

 

መደምደሚያ !

በአገራችን ምድር ሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ደግሞ ዕድገትና ስልጣኔ ዕውን እንዲሆኑ ከተፈለገ የግዴታ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለብን።  ቀድሞም ሆነ ዛሬ ያለው ችግር ራሳችንን ዘመናዊ ለማድረግ አለመቻላችንና ከአለንበት ቦታ ርቀን ለመሄድ ባለመቻላችን ነው። የፈለገውን ያህል ስለስርዓት ለውጥ ብናወራም፣ በራሳችን ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ ካላደረግንና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲመጣ ካልሞከርን  በየጊዜው ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች በድሮው የአገዛዝ ስልት በመቀጠል አሁንም ዕድገት እንዳይመጣና መረጋጋት እንዳይኖር የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ ነው ። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በግለሰቦች ቆራጥነትና ተከታታይነት ባለው ምርመራ ብቻ ነው። በየታሪክ ወቅት ብቅ ብቅ ያሉ ፈላስፋዎችን፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የፖለቲካና የመንግስት ምንነት ተመራማሪዎችን እንደዚህ አድርጉ ብሎ ማንም ያስገደዳቸው ኃይል አልነበረም። ሶክራተስን፣ ፕላቶንን፣ አሪስቶተለስንና አርቺሜዲስን ማንም የውጭ ኃይል ያስገደዳቸው አልነበረም። እንደዚሁም የሬናሳንስ ሰዎችን፣ እነዳንቴን፣ ጋሊልዮን፣ ፔትራርካንና ዳቢንቺን ማንም አላስገደዳቸውም። ከዚያም በኋላ በጀርመን ምድር እንደ አሸን የፈለቁትን እነ ኬፕለርን፣ ላይብኒዝን፣ ካንትንና ሄገልን እንዲሁም ሺለርንና ጋውክን፣ ሪማንን ማንም አላስገደዳቸውም። እነዚህ ሁሉ ለስልጣኔ መሰረት የጣሉ ኃይሎች በራሳቸው ውስጣዊ ኃይል ብቻ በመገፋፋት ነው ለአገሮቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ የሚጠቅም ወይም ዩኒቨርሳል ዕውቀት ያፈለቁትና ያስፋፉት። በዚህም መልክ ነው ለሰለጠነ መንግስትና ፖለቲካ፣ እንዲሁም ማሀበረሰብ አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታዎች አዘጋጅተው ያለፉትና በታሪክም ሲታወሱ የሚኖሩት። በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው በአንድ አገር ውስጥ ዕውነተኛ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በግለሰብ ታታሪዎች አማካይነት ሲሆን እዚህና እዚያ ተሰበጣጥረው የተለያየ ዕውቀትን የሚያፈልቁና የስልጣኔ መመሪያ እንዲሆን የሚታገሉ ኃይሎች የሃሳብ አንድነት(Unity of Thought) እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። በጀርመን ምድር ስልጣኔ ሊመጣ የቻለው በፈለሳፋዎችና በሳይንሳንቲስቶች እንዲሁም የተለያየው ዕውቀት ባለቸው ምሁሮች ዘንድ ተመሳሳይ ዕውቀትና የሚስማሙበት ጉዳይ ስለነበር ነው። እነዚህ ምሁራን በጊዜው ያስቀደሙት ነገር የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን ሳይንሳዊውን መንገድ በመፈለግ ለዕውነት መታገልና ለሰፊው ህዝብ የተሻለ ኑሮ ለማምጣት ነው። በእነሱ ዕምነት መሰረት በአንድ አገር ውስጥ ሰላምና ስምምነት ሊሰፍኑ የሚችሉት „መስማማትና መተማመን አለብን“ ብለው በመውትወት ሳይሆን የግዴታ በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ዕውቀት ሲስፋፋ ብቻ ነው ብለው በማመን ነው። በአንድ አገር ውስጥ በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ ዕድገትና ምሁራዊ ኃይል ካለ አልፎ አልፎ አለመስማማት ቢፈጠርም ወደስምምነት ማምራቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ዛሬ በአገራችንና በውጭው ምድር የሰፈነው አለመስማማትና አለመግባባት ወይም አለመቻቻል አስፈለጊውን ምሁራዊ ዝግጅት ለማድረግ ባለመቻላችንና፣ ሁላችንም በየፊናችን የዚህ ወይም የዚያ ድርጅት ደጋፊዎች በመሆን አብዛኛውን ጊዜ የልዩነታችን ነጥቦች ሳይገቡን በመጠላለፋችን ነው። በሌላ አነጋገር፣ የሁላችንም ዋና ዓላማ በአገራችን ምድር ስላምና ዕድገት እንዲሰፍኑ የምንታገል ከሆነ፣ የሰለጠነ ሲቪልና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ ከፈለግን በመሰረቱ ምንም የሚያጣላን ነገር አልነበረም።  ችግሩ ግን ከፍተኛ አለመግባባት አለ። ሁሉም በየፊናው በራሱ ዓለም ውስጥ ይሽከረከራል። በሃሳብ ዙሪያ ከመታገል ሁሉም በየጊዜው „አዳዲስ ሃሳቦች“ በመፃፍ የባሰውኑ ግራ እንድንጋባ ያደርገናል።

ያም ሆነ ይህ ስለፖለቲካ ሳይንሳዊነትና ፖለቲካም እንደ ሂሳብ መታየት አለበት ብለን ስንነሳና ስንጽፍ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማያያዝ አለብን። የሰው ልጅ ዕድገት ሁለንታዊ በሆነ መልክ መታየት ያለበት ጉዳይ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተጣመመና ጨቋኝ ኃይል ስልጣንን እስከያዘ ጊዜ ድረስ ብዙ ነገሮችን እንደሚያበላሽ ቢያንስ ከአገራችን የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ታሪክ የምንማረው ሀቅ ነው። እንደነዚህ ዐይነት ሰይጣናዊ ኃይሎች አገርን ሳያጠፉ ከስልጣን እንደማይወርዱ ከጀርመኑ የሂትለር አገዛዝ የሰማነውና በዶኩሜንተሪ ፊልም ያየነው ሃቅ ነው። ስለሆነም በአገራችን ምድር ላይ ስልጣንን የተቆናጠጠው የወያኔ አገዛዝና ግብረአበሮቹ ራሳቸውን ያሻሽላሉ፣ የፖለቲካውንም መድረክ ክፍት ያደርጋሉ የሚለው አስተሳሰብ አሳሳች ብቻ ሳይሆን የድህነቱንና የጭቆናው ዘመን እንዲራዘም የሚያደርግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው። በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ ስልጣኔና ዕድገት ዕውን እንዲሆኑ የምንመኝ ከሆነ፣ ሲቪልና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆኑ ፍላጎታችን ከሆኑ፣ ምኞታችንና ህልማችን ዕውን ሊሆኑ የሚችሉት ከዛሬው አገዛዝ ባሻገር እንደሆነ መታወቅ አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘው አንድ ነገር ብቻ ነው። ከዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አገዛዝና ተንኮልን ተግባሩ በማድረግ አገርን ከሚያከረባብት አገዛዝ ተላቆ የበለጸገና ሰላም የሰፈነበት አገር መገንባት ነው። ምኞቱና ህልሙ ከዚህ ውጭ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም።

 

                                               ፈቃዱ በቀለ

                                        fekadubekele@gmx.de