[gtranslate]

 

ሀቁን መፈለግ ወይስ ሀቁን መናገር-ከአምልኮ አስተሳሰብ

ወደ አርቆ-አሳቢነትና ወደ ሳይንሳዊ አመለካከት-

ክፍል ፪

 

                                                 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

       መግቢያ

       ፕሮፌሰር ሀይለማርያም ሀቁን መናገር ብሎ በተከታታይ አምስት ጽሁፎች ካወጣ በኋላ እኔም እንደ አቅሚቲ ለዚህ የሚሆን መልስ ስጽፍ ውይይታችንና ክርክራችን በዚያው ተከታታይነት ባለው መልክ ይቀጥላል ብዬ ገምቼ ነበር። ፕሮፌሰር ሀይለማርያምና እኔ ብቻ ሳንሆን፣ ሌሎችም በመሳተፍ የውይይታችንና የክርክራችንን አድማስ ያሰፉታል የሚል ዕምነት ነበረኝ። ይሁንና ግን እንደገመትኩት ሁላችንም በውይይቱ ልንገፋበት አልቃጣንም። በኛ ኢትዮጵያውን ምሁራን ዘንድ አንድ እንደ ፈሊጥ የተያዘ የአሰራር ስልት አለ። ይኸውም አንድን አርዕስት እስከመጨረሻው ሳይገፋበትና መቋጠሪያ ሳያገኝ ወደ ሌላ አርዕስት በመሸጋገር የመጀመሪያው እንዲረሳ ማድረግ ነው። ሁለተኛ፣ እንደዚህ ዐይነት ህብረተሰብን የሚጠቅምና ለህብረተሰብ መገንቢያ የሚያገለግል አርዕስት ሲጻፍ፣  ሁለት ወይንም ሶስት ሰዎች ብቻ እንዲከራከሩበት መንገዱን ለእነሱ ብቻ በመልቀቅ ምሁራዊ ኃይል ሰፋ እንዳይልና አስተሳሰባችንም ጥልቀትና መሰረት እንዳይዝ በር መዝጋት እንደባህል ተወስዷል። በእዚህ ጸሀፊ ዕምነት፣ ከሚደርሱኝ ደብዳቤዎች እንደምረዳው ከሆነ ብዙ አዋቂዎች እንዳሉ ነው። እነዚህም ሆኑ ሌሎች ምሁራን ምንም የሚያስፈራቸው ነገር የለም። ብዕራቸውን በማንሳትና ሃሳባቸውን በመሰንዘር ሌሎችም ሆኑ እኔ የምንጽፈውን መፈተሸና ለፈተና ማቅረብ መቻል አለባቸው። አንድ አስተሳሰብ ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት መፈተን፣ መፈተሸና መመርመር አለበት። ይህ ፕላቶናዊ የአሰራረር ስልት ነው።

       አንድ ህብረተሰብ የተወሳሰበ እንደመሆኑ መጠንና፣ በየጊዜውም  በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አዳዲስ ችግሮች ስለሚከሰቱና ባለው ላይ ተደርበው ለመፍታት ስለማያስችግሩ፣ ለምን ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንደሚያቅትና፣ አዳዲሶችንም በመፍጠር ወደ ባሰ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ እንደሚከተን የመመርመሩና መፍትሄ የመፈለጉ ጉዳይ ምሁራን ነን በምንል ትከሻ ላይ የወደቀ የታሪክና የሞራል ኃላፊነት ነው። በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ምሁራን አዳዲስ ችግሮች ሲከሰቱም ሆነ ያሉት ችግሮች ለምን እንደማይፈቱ ጥያቄ የማያቀርቡና አማራጭም የማይሰጡ ከሆነ የታሪክን ኃላፊነትንና ህዝባቸው የሚጠብቅባቸውን ግዴታቸውን ሊወጡ አይችሉም ማለት ነው። ፕሮፌሰር ሀይለማርያም አንድ ያነሳው ቁም ነገር አለ። ምሁር ለህዘቡ ብርሃን ነው የሚል ነው። ስለዚህም አንድ የምሁር ትውልድ ለህዝቡ አለኝታና ብርሃን መሆኑን ለማስመስከር ከፈለገ የግዴታ፣ ግዴታውን መወጣት አለበት። በሌላ ወገን ግን ምሁር ነኝ የሚል ሁሉ ለህዝቡ ብርሃን ሊሆን እንደማይችል፣ እንዲያውም የባሰ ወደ ጨለማ ውስጥ እንደሚከተው ከአገራችንም ሆነ ከብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው ከሚጠሩ አገሮች የምናየውና የምንማረው ሀቅ ነው። ስለዚህም አንድ የምሁር ትውልድ ያስተማረውን ህዝብ ወደ ዘለዓለማዊ ጨለማ ኑሮ ውስጥ ከቶ ፍዳ እንዳያሳየው ከተፈለገ የነቁ ምሁራን ገፋ ብለው በመሄድና ጠልቀው በመመራመር፣ ለራሱ ዝናና ጥቅም፣ እንዲሁም ለህዝብ ብሎ በቆመው መሀከል ያለውን ልዩነት ማሳየት አለባቸው። ታላቁ የጀርመን የድራማ፣ የግጥም፣ የፍልስፍናና የታሪክ ምሁር ፍሪድሪሽ ሺለር የሚባለው፣ What Is and to What End Do We Study, Universal History? በሚለው ግሩም በሆነው ጽሁፉ ውስጥ፣ ለዳቦ ብሎ የተማረና ታሪክን ለመስራት በተማረ መሀከል ያለውን ልዩነት ሲያሳይ፣ ለዳቦ ብሎ የተማረው ለራሱ ዝና ብቻና የራሱን የኑሮ ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሯሯጥ፣ በፍልስፍና የታነጸው ምሁር ግን ከራሱ ጥቅም ተሻግሮ በመሄድ በተለያዩ የሳይንስ ክፍሎች መሀከል ግኑኝነቶች እንዳሉ በመረዳት አርቆና አርቅቆ በማሰብ ጥሩ ነገር ለመስራት ቀን ከሌሊት ይታገላል ይላል። በሺለርም አነጋገር፣ „ Where the bread-fed scholar severs, the philosophical mind unites. He early convinced himself, that everything is intertwined in the field of understanding as well as in the material world, and his zealous drive for harmony cannot be satisfied with fragments of the whole.”

       ስለዚህም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተፈጠረን ምሁር ለአንድ ዓላማ እንደተሰለፈና ሁሉም ለህዝብ ተቆርቋሪ አድርጎ መውሰድ ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ሊፋቅ የማይችል የታሪክ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። ስለሆነም እኛ ነቃን የምንል ምሁሮች ሳንፈራና በይሉኝታ ሳንታሰር፣ አንድ ሙያን ወይም በአንድ የትምህርት ዘርፍ በሰለጠኑ ምሁራን መሀከል የአስተሳሰብና ችግሮችን የመረዳትና መፍትሄም የመስጠት ልዩነት ሊኖር እንደሚችል በመገንዘብ መንገዱን ሳንዘጋ ለመወያየትና ለመከራከር እንዲያም ሲል አንዱ ከሌላው ሊማር እንዲችል በተቻለ መጠን በቀና መልክ ጥረት ማድረግ አለብን። ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ከመግባቴ በፊት በመጀመሪያው እትሜ ላይ ዕውነትን ወይም ሀቅን በመፈለግ መሀከል ከህብረተሰብአችን ሁኔታ በመነሳት የተነተንኳቸው ነገሮች ስላሉ አለመግባባት እንዳይፈጠርና ጥርጣሬን ለማስወገድ እንዲቻል ከሳይንስ አንጻር ዕውነትን መፈለግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በመጠኑም ቢሆን ላብራራ።

ዕውነትን ወይም ሀቅን መፈለግ ማለት ምን ማለት ነው?

       አንዳንድ ሰዎች ሰለ ዕውነት ወይም ስለ ሀቅ መናገር ሲነሳ ትዝ የሚላቸው፣ አንድ ሰው የሰራውን መጥፎ ድርጊት ወይም ወንጀል ወደ ውጭ አውጥቶ መናገር እንዳለበት ወይም የሌላውን ሰው ድርጊት እንዲጠቁምላቸው ከዚያ ጋር በማያያዝ ነው። ይህ ሰው ውሸተኛ ነው ሲሉ፣ ያላደረገውን ነገር አድርጌያለሁ ብሎ ያወራል ማለታቸው እንጂ ከሳይንስ አንፃር ለኑሮ ትርጉም የሚሆንን የተሳሳተውን ከሀቀኛው መንገድ በመለየትና በማስረዳት የሰውየውን የተሳሳተ አቀራረብ በመተርጎም አይደለም የዕውነትን ትርጉም ለማስረዳት የሚሞክሩት። እንደዚህ ዐይነቱ ውንጀላ ወይም ሰውን መጠቆም ሳይንሳዊ ትርጉም ስሌለለው ምሁራን ነን ባዮች የግዴታ መሸሸ አለባቸው። በተጨማሪም በውንጀላ ስራ የተሰማሩትንና አገርን በማውደም የተሰለፉትን ሰዎች የመክሰስና የመወንጀሉ ጉዳይ ለሳይንስና ለስልጣኔ እንታገላለን የሚሉ ምሁራን ተግባር ሳይሆን፣ በዚህ ሙያ የሰለጠኑ የሚመለከታቸው ኢንስቲቱሽኖችና የህግ ተመራማሪዎች ተግባር ስለሆነ በእንደዚህ ያለ ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት ከቁም ነገር የሚያዘናጋ ይሆናል።  ለህብረተሰብ ግንባታ ወይም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ በሚጠቅመው ሀቁን የመፈለጉ ጉዳይና በተራ አነጋገር መሀከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ማስቀመጥ የግዴታ የምሁራን ተግባርና ሃላፊነት ነው። ስለዚህም የማንኛውም ምሁር ተግባር ራሱን መመርመርና ለህብረተሰብ ግንባታ በሚጠቅመውና በማይጠቅመው መሀከል ያለውን ዕውነትን የመፈለጉና ወደ ውጭ አውጥቶ ሌላው እንዲወያይበትና እንዲከራከርበት የማድረጉ ተግባር ሳይንሳዊ ዕውነትን የመፈለግ መንገድ ነው ብል ስህተት አይሆንም።

       ከህብረተሰብ ታሪክ አንጻር በአንድ የተወሰነ የታሪክ ወቅት ውስጥ በዚያ የሰፈነው አገዛዝና የህብረተሰቡ አኗኗር እንደ ዕውነት ተደርጎ የሚወሰድበትና ስርዓቱን፣ አገዛዙና ከአገዛዙ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ምሁራን ነን ባዮች ህዝቡ ስርዓቱን ከጭንቅላቱ ጋር እንዲያዋህደው ይሰብካሉ። በየቀኑ ሲሰበክም፣ በተለይም በወጣቱ ጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽና አብሮ በማደግ ግራና ቀኝ ዞር ብሎ እንዳያስብ ይጋረዳል። ለምሳሌ በፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያ አጼ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያን ለመግዛት ከእግዚአብሄር ተልከው የመጡ ናቸው፤ ሰማይና ንጉስ አይከሰሱም፤ ንጉሱም የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ እየተባለ ይሰበክ ነበር። ሁሉም ነገር ሊደረግ የሚችለው በንጉሱ ፈቃድ ብቻ ነበር። ሌላው ተራ ነው የሚባለው ሰፊ ህዝብ የማሰብ፣ ጥያቄ የመጠየቅና ከዚያ የተሻለ ኑሮ መኖር እንዳለበት የመታገል መብት አልነበረውም። ንጉሱ ያላደረጉትን ድርጊት ሁሉ እንዳደረጉ ስለሚሰበክ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ሃምሳ ዐመታት ያህል የሚጠጋ እንደዛሬው ዐይነቱ ስቃይ ጋር ባይወዳደርም፣ ሊሰራ የሚችላቸውን ነገሮች ሁሉ ተግባራዊ እንዳያደርግ ታገደ። በመሆኑም ንጉሳዊ አገዛዙም ሆነ ህዝቡ በህብረተሰቡ ውስጥ በየጊዜው ለውጦች መኖርና የተበላሹም ነገሮች መሻሻል እንደሌለባቸው አሜን ብለው በመቀበል ለተከታዩ ትውልድ በቀላሉ ሊሸከመው የማይችል ጭነት አሸክመውት አለፉ።

       እንደዚህ ዐይነቱ በርዕዮተ-ዓለም መታወርና ያለውን ስርዓት አሜን ብሎ መቀበል ሌሎችን ትተን በብዙ በእስላም አገዛዝ ስር በሚማቅቁ ስርዓቶች ውስጥ እናያለን። የእስልምና ሃይማኖት፣ ሃይማኖት ብቻ መሆኑ  ቀርቶ እንደ ስርዓትም እንዲወሰድ በመደረጉ አብዛኛው ህዝብ የኑሮ ፍልስፍናውን ከሃይማኖት ጋር በማዋሀድ የአገዛዙ ሰለባ እንዲሆን በቃ። በተለይም በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የእስልምና ሃይማኖት ወደ አክራሪነት በመለወጥ በተለይም የሴቶችን ነጻነት የሚቀናቀን ሆነ። በአንጻሩ ግን መሪዎቹ አገራቸው ውስጥ እንደዚህ መደረግ የለበትም እያሉ፣ በተለይም በወጣቱ ላይ ማዕቀብ ሲያሳድሩ እነሱ ግን ውጭ እየወጡ ይባልጋሉ። እንደ ካቶሊክ ሃይማኖት የመሰሉትም የተፈጥሮን ህግ የሚጻረር ህግ በማውጣት በተለይም በቄስ ወንዶችና ሴቶች መሀከል ሊኖር የሚገባውን ተፈጥሮአዊ ግኑኝነት እንደ ሃጢአት በመቁጠር የሰው ልጅ የኑሮ ትርጉም እንዳይኖረው ያደርጋሉ። ወደ ሰፊው የሃይማኖት መወዛገብም ስንመጣ በየታሪክ የዕድገት ደረጃዎች(በየኤፖኮች) ውስጥ በእስልምናና በካቶሊክ ሃይማኖት መሀከል የተደረገውን ግጭትና ዛሬም በጥርጣሬም መተያየት፣ እንዲሁም በአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች ከአስራ-አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይደረግባቸው የነበረውን ክትትልና ዕልቂት እንዲሁም መሰደድ፣ የአንደኛው ሃይማኖት ተከታዮች መሪዎች እኔ የምሰብከውና የማስተምረው ሃይማኖት ብቻ ነው ትክክል ነው ብለው ሰፊውን ህዝብ ጭንቅላቱ እንዲታወር በማድረግ በሌላ ዕምነት ተከታይ ላይ ጥላቻ እንዲያሳድርና እንዲነሳ በማድረግ ለህዝብ እልቂት ምክንያት ሆነዋል። ሌሲንግ የተባለው የአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን የጀርመኑ የድራማና የስነ-ጽሁፍ ተመራማሪ ይህንን ተገቢ ያልሆነ ቅስቀሳና ድርጊት ከተመለከተ በኋላ “ጥበበኛው ናታን” በሚለው ድራማው በሶስቱ ሃይማኖቶች መሀከል ያለው ችግር ካለመግባባት የመነጨ መሆኑን በማመልከት፣ ሁሉም በየፊናው ጥሩ ጎኖች እንዳሉት በምሳሌ በማሳየት፣ አርቆ-አስተዋይነትን በማስቀደም ተከባብረው ሊኖሩ የሚችሉቡትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው ጠቆመ። የድራማው ዋና መልዕክትም፣ ሰብአዊነት፣ የሌላውን ሃሳብ ወይም ዕምነት መቀበልን የሚያመለክት ሲሆን፣ በተገለጸ-አስተሳሰብ(Enlightenment) ላይ የተመረኮዘ ነው። በተጨማሪም የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሄር አምላክ የተፈጠረ ስለሆነ፣ በሃይማኖት ተከፋፍለው አንደኛው የክርስቲያን ዕምነት ተከታይ፣ ሌላው ደግሞ የይሁዲ፣ የተቀረው ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን እግዚአብሄር ሁሉንም በእኩል ዐይን በማየት አድልዎ እንደማያደርግና እንደማያውቅም የሚያስረዳ ነው። ሶስቱም የተለያያ ስም ቢይዙም የታሪክ አመጣጣቸው አንድ ምንጭ ነው። ስለዚህም በሶስቱ የሃይማኖት ዕምነት ተከታዮች መሀከል ጠብ የሚያስጭር ምንም ምክንያት የለም። በሌላ አነጋገር ሁሉም በየፊናው እኔ ነኝ ትክክለኛ ብሎ ግትር ያለ አቋም ከወሰደ የመጨረሻ መጨረሻ መተላለቅና ትልቅ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ ሊነሳ እንደሚችል በመገንዘቡ፣ ሁሉም ተከባብረውና ተባብረው ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታና አገር በማሰብ ኃይላቸው ሊገነቡ እንደሚችሉ አመለከተ።

       ይህ ጭፍን አመለካከትና የኔ ብቻ ነው ትክክል ብሎ ሌላው እንድያመነውና እንዲቀበለው መታገልና በሌላው አስተሳሰብ ላይ በሳይንስ ላይ ያልተመረኮዘ ውንጀላና ጥላቻ ማካሄድ ለዕውነተኛ ዕውቀት እንዲያም ሲል ለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ሰፋ ላለ ስልጣኔ የሚደረገውን ትግል ከመጀመሪያውኑ ይገታል። እንደዚህ ዐይነቱ ጭፍን ዕምነት አንድ ዝሆን ጋ ቀርበው ምን ዐይነት እንስሳ መሆኑን እንዲነግሩ የተጠየቁትን የብዙ ዕውር ሰዎችን ታሪክ ያስታውሰናል። ዕውሮቹ ዝሆን ምን እንደሚመስል ስለማያውቁ፣ ምን ዐይነት እንስሳ እንደሆነ እንዲነግሩ ተራ በተራ ይጠየቃሉ። የመጀመሪያው ጅራቱን ከዳሰሰ በኋላ ገመድ ይመስላል ይላል። ሁለተኛው ደግሞ፣ አንድ ጎኑን ከዳሰሰ በኋላ ግድግዳ ይመስላል ብሎ ይናገራል። እግሩን የዳሰሰው ሶስተኛው ደግሞ፣ ዛፉ የተቆረጠለት ስር ይመስላል ይላል። አራተኛው ደግሞ ኩንቢውን ከነካ በኋላ እባብ ነው ብሎ ይናገራል። በርዕዮተ-ዓለም ወይም በጥላቻ አዕምሮአቸው የተሸፈኑ ሰዎችም የዓለምን ሁኔታ እንደዕውሮቹ በተወሰነ ነገር ላይ ብቻ በማትኮር የማሰብ አድማሳቸውን ያጠባሉ። እነሱ ጭንቅላታቸው ውስጥ በቀረጹት አስተሳሰብ በመታወር፣ በተወሳሰበው የዓለም ሁኔታና ተጨባጭ ነገርና በራሳቻው ቁንጽል አስተሳሰብ መሀከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ሊረዱ አይችሉም። አንድን የህብረተሰብ አወቃቀርና በውስጡ ያሉትን የተወሳሰቡ ነገሮች ለመገንዘብ ከብዙ አንፃር መመልከትና መመርምር እንዳለባቸው ጥረት አያደርጉም።

       ወደ ትምህርትም ዓለም፣ በተለይ ወደ ህብረተሰብ ሳይንስ ስንመጣ ያለው ውዝግብ ልክ ሃይማኖትን ይመስላል። በተለይም ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚባለው የኢኮኖሚክስ አንድ ክፍል የበላይነትን በተቀዳጀበት ዘመንና ዓለም-አቀፋዊነት ባህርይ ይዞ በሁሉም አገር የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ከገባ ወዲህ፣ በዚህ የሰለጠነ አካዳሚሺያን፣ ኢኮኖሚክስ ሲባል ይህ ብቻ የሚመስለውና ዐይኑን አፍጦ የሚከራከር ብዙ ነው። የኢኮኖሚስ ቲዎሪን ዕድገት አመጣጥና በምንስ ርዕዮተ-ዓለም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ሳይገነዘብና ሳያጠና እንደ አዋቂ ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል።  በዚህ ዐይነቱ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ተነጥሎ “በረቀቀ ቲዎሪ” የሰለጠነ አካዳሚሺያን ቲዎሪውን ከመስበኩና ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት አንድ ቦታ ላይ ቆሞ የተማረው ትምህርት በዕርግጥስ ዕውነት መሆኑና ለችግርም መፍቺያ እንደ ፍቱን መሳሪያ ሊያገለግል ይችላል ብሎ ራሱን አይጠይቅም። ለምሳሌ በተደጋጋሚ እዚያው በዚያው በኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚክ ፖሊሲ መሰረት ከሃያ ዓመት ጀምሮ የአንድ አገር የኢኮኖሚ ችግር እንዲፈታ ፖሊሲ ሲነደፍና ተግባራዊ ሲሆን፣ ከጥሩ ውጤት ይልቅ ቀውስ ሲፈጠርና፣ እንደገና በሌላ መልክ ያው ፖሊሲ ከአምስት ዓመት በኋላ ተግባራዊ ሲሆን ለምንድ ነው ይህ ነገር ከመፍትሄ ይልቅ ችግር ውስጥ የሚከተን? ብሎ ደፍሮ ራሱን የሚጠይቅና አማራጭ ፖሊሲ ለመፈለግ የሚጥር የለም። እንደዚህ ዐይነቱ አካዴሚሺያን ብርሃን ከመሆን ይልቅ ራሱ ጨለማ ሆኖ የሚሊዮን ህዝብ ኑሮ እንዲጨልም ያደርጋል። ዛሬ በአገራችንም ሆነ በብዙ አፍሪቃ አገሮች የምናየው ይህንን በአንድ ወጥ ፖሊሲ በመታወርና በመመራት የብዙ መቶ ሚሊዮንን ህዝቦች ዕድል ማጨለምና እየተሰደዱ እንዲኖሩ ማድረግ ነው።

       የብዙዎቹ በህብረተሰብ ሳይንስ፣ በተለይም በኒዎ-ሊበራሊዝም የሰለጠኑ ምሁራን ችግር አንድ ድርጊት በአንድ ወቅት እንደሚከናወንና በትላንት፣ በዛሬና በነገ መሀከል የሚኖረውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት በፍጹም ለመረዳት ያለመቻል ነው። ለምሳሌ የዛሬው በብዙ የካፒታሊስት አገሮች የሰፈነው የኢኮኖሚ ስርዓት ቢያንስ የአራት መቶ ዓመት ዕድሜ እንደ ነበረውና፣ በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ ምን ያህል ህብረተሰብአዊ ውዝግቦችና ቀስ በቀስ ደግሞ መዳላደልና ተቀባይነት እንዲያገኝ  መሰበክ እንደተጀመረ በፍጹም አይረዱም። በኔዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት፣ የጥሬ-ሀብት የተመጠነ ነው ወይም እንደልብ አይገኝም፤ የዕቃዎች ዋጋ በገበያ ላይ በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል የሚደነገግ ነው፤ በገበያ ላይ የሚሳተፍ ሁሉ ተመሳሳይና የተሟላ ኢንፎርሜሽን አለው፤ በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ተጠቃሚም፣ በዕቃዎችም ሆነ በምግብ ውስጥ ምን ምን ነገሮች እንዳሉ በደንብ ያውቃል፤ አምራችና ሺያጭ ተጠቃሚውን በማስታወቂያ ሊያጭበረብረው አይችልም… ወዘተ. ብሎ በትምህርት ቤት ስለሚሰበክ፣ በተለይም አንድ ከአፍሪቃ የመጣን ወይም አገሩ ውስጥ የሚማርን ተማሪ ሊያሳስተው ይችላል። ዕውነትን ከውሸት ሊለይ እንዳይችል ከመጀመሪያውኑ ጭንቅላቱ ስለሚጋረድ፣ እሱን እንደሳይንስና እንደህብረተሰብ ችግር መፍቻ በመውሰድና ተግባራዊ በማድረግ ምስቅልቅል ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። በዚህም ምክንያት አንድ ምሁር ማድረግ ያለበትን፣ ማድረግ እንዳይችል ጭንቅላቱ ይጋረዳል።

       ይህንን በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል። ለምሳሌ የራሳችንን ሁኔታ ስንወስድ በዚህም በዚያም ብለን አምልጠን እዚህ የደረስን ከብዙ አደጋዎችና በሽታዎች ካመለጥን በኋላ ነው። ከህጻንነታችን ወይም ትንሽ ነፍስ ካወቅን በኋላ ወደፊት ተምሬ እንደዚህ እሆናለሁ ብለን ካሰብነው ውስጥ የተመኘነውን የተቀዳጀነው፣ ምናልባት በጣም በጣት የምንቆጠር ብንገኝ ነው። ዛሬ ወደደረስንበት ደረጃ፣ መጥፎም ይሁን ጥሩ፣ የተወለድነበት የቤተሰብ ሁኔታ፣ የቤተሰቦቻችን የትምህርት ደረጃና የማሰብ ኃይል፣ እንዲሁም የጠቅላላው የህብረተሰብአችን የባህል ዕድገት ሁኔታ ይወስናሉ። ብዙ ነገሮች ቢሟሉ እንኳ፣ በህይወት ውስጥ ዕድል ወይም አጋጣሚ የሚባል ነገር አለ። ለመኖራችንና እዚህ ደረጃም ለመድረሳችን ከቀድሞውኑ እኛ የወሰነው አይደለም። ተፈጥሮ የማጣራት ህግ ወይም መሳሪያዎች እንደሏት ሁሉ የሰውም ልጅ ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ መድረስ ከላይ ሁኔታ ከጠቀሰው ባሻገር ዕድልና አጋጣሚ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። አንድ ቦታ ለመድረስ የራስ ጥረትና ከመጥፎ ነገሮች መቆጠብ ወሳኝ ሚናን ቢጫወቱም ዕድልና አጋጣሚ የሚባሉት ነገሮች ለአንድ ነገር መሳካት አስፈላጊ መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። ይህንን ወደ ህብረተሰብ ግንባታ ስንለውጠው ከላይ እንዳልኩት የዛሬው የካፒታሊስት ስርዓት እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው የኒዎ-ሊበራል ተመጻዳቂዎች እንደሚሉት በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ሳይሆን ብዙ ሺህ ነገሮች በአጋጣሚም ሆነ በማወቅ በመገናኘት ብዙ ችግር ከታለፈ በኋላ የተደረሰበት ሰርዓት ነው። እንደዚሁም የኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሆኖ ከመውጣቱና ተቀባይነት እንዲያገኝ ከመደረጉ በፊት ስርዓቱን መልክ ለማሲያዝ በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ በአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በኢጣሊያን የሬናሳንስ የኢኮኖሚ ፖሊሲና እንቅስቃሴ፣ የስኮላስቲክ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ከመርካንትሊዝም እስከ ፊዝዮክራቲስና የእነ አዳም ስሚዝ ቲዎሪን አልፎ እዚህ የተደረሰበት ነው። ኒዎ-ሊበራሊዝም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1930ዎቹ ወስጥ እንደ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ቢጠቀስም መሰረቱ የተጣለው በ1880ዎቹ ዐመታት ማርጂናሊዝም በሚለው ክስተትን እንደቲዎሪ መንደፊያ ባደረገ የኢኮኖሚ ቲዎሪ አማካይነት ነው። እንዲሁም፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ራሱን ከሌሎች ነጥሎ የወጣው የማርክሲስት የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ቲዎሪ አለ። በተለይም ዳስ ካፒታልን ያነበበ፣ በተጨባጭ ነገሮችና በክስተት ላይ ተመርኩዞ የዳበረውን ቲዎሪ ልዩነቱን ሊያገናዝብ ይችላል። ያም ሆኖ፣ ኒዎ-ሊበራሊዝም አማራጭ የሌለው ፖሊሲ ሆኖ ዐይኑን አፍጦ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለው ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ፓሊሲው ደግሞ ወደ ተግባር ሲተረጎም ባለፉት ሰላሳ ዐመታት በጥብቅ እንደተከታተልነውና እንደተመራመርነው፣ እንዲሁም በብዙ ጥናቶች እንደተረጋገጠው ሀብትን ከአንዱ የህብረተሰብ ክፍል ወደ ሌላኛው ማሸጋሸጊያ እንጂ፣ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትን ለመፍጠር የሚያስችልና፣ አንድ ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን የተሻለን ኑሮ በመመስረት የህይወት አድማሱን እንዲያሰፋለት የሚያደርግ አይደለም። ሌላው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ችግር፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ ፍልስፍናን፣ የህሊናን አወቃቀርና የከተማን ግንባታን በማሰቀረት(Excluding) የአንድን ህዝብ ኑሮ ወደ ንጹህ ኢኮኖሚ ክንውን መቀነስ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ ደግሞ አንድ ሰው ከጭንቅላቱ በስተቀር ሌላ ነገር የለውም፤ የሚሰራውም፣ የሚንቀሳቀሰውምና ሁሉንም ነገር የሚያደረገው ጭንቅላቱ ብቻ በመሽከርከር ነው እንደማለት ነው። እጅና እግር እንዲሁም ልዩ ልዩ የተለያዩ ተግባራትን የሚፈጽሙ የሰውነት ክፍሎች የሉትም እንደማለት የሚቆጠር ዐይነት ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ ነው። ሌላው ችግር ደግሞ፣ የዓለም ህዝብ በሙሉ አንድ ተመሳሳይ በሽታ ስለያዘው ሊታከምና ሊድን የሚችለው በአንድ አገር በተሰራ መድሃኒት ብቻ ነው የሚል ዕምነት የተያዘው። ቀጥታ ወደ ፖሊሲው ስንመጣ ሙሉ በሙሉ የተፈጥሮን ህግ ይጻረራል። በመጀመሪያ፣ ሰው ራሱም ሆነ ተፈጥሮ እዚያው በዚያው አንድም ብዙም ናቸው። ለምሳሌ ራሳችንን ብንወስድ በአንድ በኩል እንደ አንድ ነጠላ ግለሰቦች ነን። በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ሰው ለማሰብ፣ ለመንቀሳቀስና ለመስራትም ሆነ ለመኖር የሚያገለግሉን ብዙ ኦርጋኖችና በሚሊያርድ የሚቆጠሩ ሴሎችና የነርቭ ሰርዓቶች አሉን። እያንዳንዱ የኦርጋን ክፍል ተፈጥሮ የሰጠውን የስራ ክፍፍል በማቀነባበርና ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም ከሌላው የኦርጋን ክፍል ጋር በመተጋገዝ ሰው ሆነን እንድንኖር ይረዱናል። በተጨማሪም፣ በተፈጥሮ ህግ መሰረት ማንኛውም ነገር ከታች ወደ ላይ የሚያድግ ነው። አትክልቶች፣ እንስሳዎችና ሰውም ጭምር ከትንሽ ነገር ተነስተው የተወሰኑ ነገሮች ከተሟሉ ከታች ወደ ላይ እያደጉና እየተስፋፉ ነው የሚሄዱት። ለምሳሌ አንድ ሰው፣ ሰው ከመሆኑ በፊት መወለድ አለበት። ከመወለዱ በፊት መጸነስና መረገዝ አለበት። በእናት ማህጸን ውስጥ የባዮሎጂን ክንውን ካካሄደ በኋላ መጥፎ አጋጣሚ ካልተፈጠረ በስተቀር ከዘጠኝ ወር በኋላ ይወለዳል። ለአቅመ-አዳምም የሚደርሰው ብዙ ፈተናዎችን ካለፈ በኋላ ነው። ቤትም ሲሰራ በመጀመሪያ ደረጃ መሰረት ነው እንጂ የሚዘረጋው ከጣሪያ አይጀመርም። ወደ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ስንመጣ አንድ ፋብሪካ ከመከፈቱ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያና የኃይል ጉዳይ በአንድ አካባቢ ተሟልቶ ይገኝ አይገኝ መታወቅ አለበት። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከመሟላታቸው በፊት በአንድ አካባቢ የኮካኮላ፣ የሲጋራ ወይም የስኳር ፋብሪካ አይቋቋምም። ለምሳሌ የአውሮፓውን የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ ስንመለከት፣ የጀመሩት ከሲጋራ ወይም ከመጠጥ ፋብሪካ ሳይሆን ፣ የምግብን ችግር በመፍታት፣ ከተማዎችን በመቆርቆርና የዕድ-ጥበብ ሙያን በማስፋፋትና ቤተ- ክርስቲያናትን በመስራትና የገበያ አዳራሾችን በመዘርጋት የሰውን አስተሳሰብ በመሰብሰብ ከታች ወደ ላይ የተደረገ የዕድገት ጉዞ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ስልጣኔ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ ህብረተሰብ መመሪያ ፖሊሲ አድርገን ከተቀበልን የአንድን ህብረተሰብ በስልጣኔ ወደ ኋላ-መቅረት ለመረዳት በፍጹም አንችልም። ምክንያቱም ፖሊሲው ችግርንና የችግሩን ምንጭ ከመፍትሄው ነጥሎ ማየት ስለማይችልና እዚያው በዚያው መፍትሄና ችግርን በአንድ መነጽር ስለሚመለከት ነው። በተጨማሪም የኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ አንድ ህብረተሰብ እንዴት እንደተዋቀረና በምንስ ውስጣዊ ህጎች እንደሚተዳደር ለመመርመር ያሚያስችል የቲዎሪ መሳሪያ አይደለም። አንድን  ህብረተሰብ ከክሰስተት አንጻር ብቻ የሚመለከት በመሆኑ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ወደውስጥ ገብተን እንዳንመረምር ከመጀመሪያውኑ ያግዳል።  የአንድን ህብረተሰብ ችግር ከሁሉም አኳያ(in its totality) መመርመር ካልቻልን ደግሞ መፍትሄ ሳይሆን የምናቀርበው ባለው ችግር ላይ ተጨማሪ ችግር እንዲፈጠር ነው የምንሰራው ማለት ነው። ባለፉት ስድሳ ዓመታት በብዙ ሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የተከሰቱት ኢኮኖሚያዊ፣ ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ችግሮች በሙሉ ከነጻ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ተነጥለው ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም።

       ከዚህ ስንነሳ፣ ጥቂት ሰዎች የተወሰነ ርዕዮተ-ዓለምንም ሆነ ሃይማኖት ወይም ትምህርት እንደ ህብረተሰብ ችግር መፍቻ አድርገው በመውሰድ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ ሳያወላውል እንዲቀበል በማድረግ ያሳስታሉ። በተለይም የተማረ ሰው ልዩ ክብር በሚሰጥበት እንደኛ ባለ ህብረተሰብ ውስጥ እሱ የተናገረውና ያስተማረው ነገር ሁሉ እንደ ዕውነት ተቀባይነትን ያገኛል። ህብረተሰቡ ዕውነትን ከውሸት ለመለየት ያሚያስችለው ዕውቀት ስለሌለው ተማሩ የሚባሉትን ምሁራን ምክር በመቀበል አብዛኛውን ጊዜ ገደል ውስጥ ይገባል። እንደዚህ የምለው ለምንድ ነው? በአገራችንም  ሆነ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ትችታዊ አመለካከት ስለሌለና እንደመሰረታዊ ነገርም ስለማይታይ ጥቂት ተማርን የሚሉና ስልጠና ያገኙና በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ተቀባይነት ያገኙ ምሁራን ፖሊሲዎችን በመንደፍ ህብረተሰቡን የዕውነተኛ ስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን መንገዱን ይዘጉበታል። ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር በማይሆን ፖሊሲ አማካይነት ኑሮው ጨለማ እንዲሆን በማድረግ ወደ ባርነት ይለውጡታል። ዛሬ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ የሚፈጸመው ድርጊትና ሀብትን በአገዛዞችና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር አድርጎ ወደ ውጭ ማስወጣትና ወደ ውስጥ ደግሞ ድህነትንና አቅመ-ቢሰነትን ማስፋፋት ተማርን የሚሉ ሰዎች ተግባራዊ በሚያደርጉት የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው።

       ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ስንመጣ ደግሞ፣ ታወቆም ሆነ ሳይታወቅ የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ላይ ተወርውሮ ራሱን ካወቀና ከእንስሳ መለየቱን ከተረዳ ጀምሮ ድርጊቱ ሁሉ ሳይንሳዊ ነበር ማለት ይቻላል። እሳትን ማግኘትና እህልን አብስሎ መብላት፣ መሳሪያ መስራትና በመሳሪያና በእሳት አማካይነት የተፈጥሮ ውጤቶችን ወደ ተጠቀሜታ ነገሮች መለውጥ፣ እነዚህ ሁሉ በሰፊው ሲታዩ የሰው ልጅ በተከታታይ ራሱን ለመለወጥ ትግል ያደርግ እንደነበር ነው። በዚህ መልክ በሰው ልጅና በተፈጥሮ  መሀከል ይካሄድ የነበረው ግኑኝነትና የሰው ልጅም ተፍጨርጭሮ የእርሻ ተግባርን ማካሄድና ከብትን ማርባትና ለጥቅም ማዋል፣ ከዚያም አልፎ ራሱን የሚከላከልበትንና ለምርት ክንውን የሚያገለግሉ መሳሪዎችን መስራት አብዛኛውን ጊዜ በተጠና መልክ ሳይሆን በደመ-ነፍስ በተገኘ ዕውቀት(Intuition) ወይም በግብታዊ መልክ የሚካሄድ ነበር። በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ብዙ አገሮች፣ ኢትዮጵያችንንም ጨምሮ በአንዳንድ ቴክኖሎጂዎች ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ነበራቸው። በትክክል መቼ እንደተጀመረ ባይታወቅም፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ግኑኝነት ሳይኖር በአንዳንድ አካባቢዎች የሸማኔ ስራ የተስፋፋ ነበር። እንዲሁም የካቲካላን፣ የጠላንና የጠጅን አጠማመቅ ስንመለከት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ልክ እንደ አገራችንም ይጠመቅ ነበር። ለምሳሌ የካቲካላን አጠማመቅ ስንመለከት የኬሜካልና የፊዚክስ ክንውን ነው ማለት ይቻላል። እንደዚህ ዐይነቱን ቲክኖሎጂና የአጠማመቅ ስልት ያልተማሩ ሰዎች ናቸው የፈጠሩት። ይህም የሚያሳየው የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን ፕላቶ እንዳለው ማንኛውም የሰው ልጅ ከሃሳብ ጋር የተፈጠረ መሆኑን ነው።  የሳይንስ መስረቱ ከሶስት ሺህ ዐመት ጀምሮ የተጣለ ቢሆንም፣ ሳይንስን ለቴክኖሎጂ ማፍለቂያ መጠቀም የተጀመረው ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ነው። ይህ ደግሞ ጥያቄን በመጠየቅና መላ-ምትን በማስቀመጥ፣ እንደገና በመመርመርና በመሞከር ቀስ በቀስ ወደ ተግባርነት ለመለወጥ የተደረሰበት ዘዴ ነው። ከአስትሮኖሚ ጀምሮ እስከ ጠቅላላው የፊዚክስ ዕድገት፣ ከባይሎጂና እስከ ኬሚስትሪ ድረስ የዳበሩትና ለሰው ልጅ መሳሪያዎችም መስሪያ ሆነው የተፈጥሮን ህግ በመረዳት በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች አውጥቶ ቅርጻቸውን ለውጦ ለጥቅም ማዋል፣ እነዚህ ሁሉ የመጨረሻ መጨረሻ 㔫ኑሮን ትርጉም ከመስጠት ወይም ሀቁን ለመፈለግና ለማገኝት ጥረት ከማድረግ ተነጥለው ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም። ይህም የሚያረጋግጠው የሰው ልጅ በቀጥታ ከሚያያቸው ነገሮች ተሻግሮ በመሄድ የራሱን ምንነት በማወቅና የተፈጥሮን ምስጢር ሊረዳ በመቻሉ ነው። ከብዙ መቶ ዐመታት ጀምሮ እንደ ትምህርት የሚሰጡት ትምህርቶች በሙሉ ከሰው ልጅ ጭንቅላት የፈለቁ እንጂ ከሰማይ ዱብ ያሉ አይደሉም። የሰው ልጅ የምርምርና አርቆ የማሰብ ውጤቶች ናቸው። ባጭሩ የተፈጥሮ ሳይንስም ሆነ ዕውነተኛው የህብረተሰብ ሳይንስ የሚያስተምሩን በርዕዮተ-ዓለም ሰበካና በገዢዎች ሳንታለል ራሳችንን በመጠየቅ፣ በመመራመርና በመሞከር ለዕድገት መታገል እንደሚያስፈልግ ነው። ዕውነተኛ ሳይንሳዊ ምርምሮችና አጠቃላይ ዕውቀቶች የየግለሰቦች ጥረት ውጤቶች እንጂ የየመንግስታቶች ውጤቶች እንዳይደሉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ታሪክ ያስተምረናል። በሌላ ወገን ግን መልካምና አበረታታች አስተዳደር የየግለሰቦችን ጥረት እንደሚያግዝና ለዕድገት የሚደረገውንም ርብርቦሽ እንደሚያፋጥነው በታሪክ የታወቀ ነገር ነው። በተለይም በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በፈረንሳይና በእንግሊዝ የተቋቋሙት የሳይንስ አካዳሚዎች የሚያረጋግጡት በኢንስቲቱሽን ደረጃ የሚደገፍ የየግለሰቦች ምርምርና ተባብሮ በጋራ ለመስራት አመቺ ሁኔታ መፍጠር ለስልጣኔ የሚደረገውን ያልተቆጠበ ትግል እንደሚያፋጥነው ነው። ግለሰቦች ብቻቸውን እዚህና እዚያ ቢፘፘጡ ተከታታይ ድጋፍ እስካላገኙ ድረስ ምርቃማ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል የተረዱት የአውሮፓ የፍጹም ሞናርኪዎች አገዛዝ በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጸውንና ለስልጣኔ አመቺ መሰረት ይጥላል ብለው ያመኑትን የኢንስቲቱሸን መሰረቶች  ማዋቀር ነበር ተግባራቸው። ከዚህም ባሻገር የተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ አገር ተመራማሪዎች ዕውቀታቸውን ለራሳቸው ብቻ አፍነው ለማስቀረት የሚጥሩ አልነበሩም። በእንግሊዝና በፈረንሳይ እንዲሁም በጀርመን ሳይንቲስቶች መሀከል የጠበቀና ጠለቅ ያለ የደብዳቤ ልውውጥ እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። የአካዳሚክ ሳይንስ ኢንሰቲቱሽኖችም በምርምራቸው ብቃት ላሳዩ የተለያዩ ምሁራን በሩ ክፍት ነበር። ስለሆነም ለምሳሌ የጀርመን አዋቂና ተደማጭነት ያለው የፈረንሳዩ የሳይንስ አካዳሚ አባል እንዲሆን ይደረጋል። በዚህ መልክ በተለያዩ አገር ተመራማሪዎች ዘንድ መቀናናት ሳይሆን መደጋገፍና ለጋራ ዓላማ መስራት ለአውሮፓው ስልጣኔ አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ የማይታበል ሀቅ ነው። ከዚህም ባሻገር ምሁራኑ መንግስታትን እንዲያማክሩ ጥሪ ይደረግላቸው ነበር። የሳይንቲስቶችን፣ የፈላስፋዎችን፣የክላሲካል ሙዚቃ ሊቃውንትን፣ የአርክቴክተሮችንና እንዲሁም በደንብ የተጠናን የከተማ ዕቅድ ዕውቀት ያላቸውን ተመራማሪዎች ዕውቀት የተረዱት የአውሮፓ የፍጹም ሞናርኪዎች ለምሁራኑ ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ ይሰጧቸው እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። ዕውነትን ለመፈለግ በሚደረገው ጥረት ፍልስፍና መሰረታዊ ቦታ ሲኖረው፣ በፍልስፍና አማካይነት የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች እንዴት እንደተሳሰሩ መገንዘብ እንችላለን። አንዳንድ ዕውቀቶች ከሌላው ተነጥለው የሚታዩ ቢመስሉም ጠጋ ብለን ስንመለከት በተለያዩ ዕውቀቶች መሀከል መተሳሰር እንዳለ መረዳት እንችላለን። ይህንን ስንረዳም ለስልጣኔ የሚደረገው ትግል ግልጽ ይሆናል ማለት ነው። በማሰብ ኃይላችንም የተፈጥሮን ምስጢር ስንረዳ፣ የኑሮም  ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። ሰላምና ጥበብ የሰፈነበት ህብረተሰብም ለመመስረት የሚደረገው ትግል የተቃና ይሆናል። ባጭሩ ዕውነቱን ስለመፈለግ ስናወራ ወይም ዕውነት ማለት ምን ማለት ነው? ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ የትግላችንም ዓላማ ግልጽ ይሆናል። ዕውነት ንጽጽራዊ(Relative) መሆኑን ስንገነዘብ ከመንፈሳዊ ጭንቀት በመላቀቅ ፍሬያማ ነገር መስራት እንችላለን። ይህንን ይበልጥ ለመረዳት ከአምልኮአዊ አስተሳሰብ ወደ ሳይንስ የተደረገውን ትግል ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል። ከዚያ በፊት ግን በአፍሪቃ ምድር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ገርደፍ ገርደፍ እያደረግን እንመልከት።

የአፍሪቃ ምሁራን ችግር- ዕውነትን በመፈለግና በዕውነተኛው ዕውቀት መሀከል ያለውን መተሳሰር ያለመረዳት !

                ፕሮፌሰር ሀይለማርያም ሀቁን መናገር በሚለው በተከታታይ ባወጣቸው ጽሁፎች ውስጥ የአፍሪቃ ምሁራን ስላላቸው አሉታዊ ሚና ወይም ደግሞ በአገሮቻቸው ውስጥ የሰፈኑትን መጥፎ ሁኔታዎች ዝም ብለው እንደሚመለከቱ አለፍ አለፍ እያለ ለማተት ሞክሯል። በእኔ ዕምነት ግን ሀተታው የታሪክን ሂደት ሊያገናዝብ የቻለ አይመስለኝም። በዕውቀትና በባህላዊ ተሀድሶ መሀከል ሊኖር የሚችለውን ውስጣዊ ግኑኝነት ጠጋ ብሎ የተመለከተ አቀራረብ አይደለም።

       እንደሚታወቀውና በብዙ ማስረጃዎችም እንደተደገፈው፣ ግሪኮች የፍልስፍናንም ሆነ የሂሳብን ዕውቀት ከግብጽ እንደወሰዱና እንዳስፋፉ ነው። የግብጽ ፋራኦኖችም ሆኑ ቄሶች አንዳንድ የአውሮፓ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ነጮች ሳይሆኑ ጥቁሮች እንደነበሩ፣ በተለይም በፕሮፌሰር አንታይ ድዮፕ ቆዳቸውን ሁሉ በመመርመር ተረጋግጧል። በጥናቱም መሰረት ግሪኮች ልዩ ልዩ የአምላኮች ስሞቻቸውን ከግብጽ እንደወረሱና ፍልስፍናና ስልጣኔም ከግብጽ እንደመጡ፣ “አፍሪቃ የአውሮፓው የስልጣኔ እናት” በሚለው ግሩም መጽሀፋቸው ያትታሉ። በርናል የተባለውም ይሁዳዊ የታሪክ ተመራማሪ “ብላክ አቴና” በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ግሪክ የግብጽ ቅኝ ግዛት እንደነበረችና ጥቁሮችም ለስልጣኔው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አረጋግጧል። የግብጽ ሚና እስካሁንም የሚያከራክርና፣ በተለይም ወደ ዘረኝነት በማምራት ጥቁር ይህንን ዐይነቱን ስልጣኔ ሊፈጥር አይችልም እየተባለ ይወራል። እንዲያውም አልፎ ተርፎ አሁንም ተመራምረን ደረስንበት በሚለው እጅግ የተሳሳተ አቀራረባቸው፣ የጀርመን ተመራማሪዎች እዚህ በጀርመን አገር ላይብዚግ በሚባል ከተማ፣ ማሰብ፣ ስሜትና ርህሩህነት እንዲሁም ሰብአዊነት የነጭ ዘርና የአሲያቶች ባህርዮች ብቻ ናቸው በማለት የጥቁር ህዝብ እነዚህ ማንኛውም የሰው ልጅ ባህርዮች ሊኖረው አይችልም ወደሚለው አባባል በማምራት የቱን ያህል የውስጥ ለውስጥ ዘርኝነትን እንደሚያሰፋፉ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ብዙ የማዕከለኛውን አውሮፓ አገሮች ያሰለጠኑ ሮማውያን ናቸው። ከተማዎች፣ ትላልቅ ህንጻዎችን፣ መፋሰሻዎችንና የእርሻ ተግባር በብዙ አውሮፓ አገሮች፣ በተለይም በደቡብና በምዕራቡ የጀርመን ክፍል ሮማውያን ናቸው የገነቡና ያስፋፉ። ጀርመኖች አዳዲስ በተቆረቆሩና በተገነቡ ከተሞች ውስጥ መግባት አይፈቀድላቸውም ነበር። ጀርመኖች ያልሰለጠኑ ስለነበሩ በደረሱበት ቦታ ሁሉ ሮማውያን የገነቧቸውን ከተማዎች ያፈራርሱ ነበር። የኋላ ኋላ ነው እየተማሩና አስፈላጊነቱን እየተረዱ የመጡት። በሁለተኛ ደረጃ፣ ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የዳበረው የሰብአዊነት አስተሳሰብና እንቅስቃሴ ከግሪኩ እንዲያም ሲል ከግብጹ ስልጣኔ ውጭ ተነጥሎ ሊታይ እንደማይቻል ብዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በጥናቶችም መሰረት፣ የሰው ልጅ ልዩ ልዩ ጥሩ ባህርዮች ወደ ውጭ ሊወጡና ሊዳብሩ የሚችሉት የባህል ለውጥ ከተደረገ ብቻ እንደሆነ ነው። በተጨማሪም፣ የአውሮፓን ታሪክ በጥብቅ ለተከታተለ፣ ሴቶችን ልዩ ፍጡሮች ናቸው ብሎ ማሳደድና ማቃጠል፣ ከማንኛውም የወንዶች ማህበሮች ማስወገድ ወይም እንዳይገቡ መከልከል፣ ሃይማኖትን አሳቦ እርስ በርስ መተላለቅ፣ በተለይም የገዢው መደቦችና የጥቂት ምሁራን  ባህርዮች እንደነበሩ ማረጋገጥ ይቻላል። ከዚህም በላይ፣ በፈረንሳይና በእንግሊዝ ሳያቋርጥ የተካሄደው የመቶ ዐመት ጦርነት፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች መሀከል የተካሄደው የርስ በርስ መጨፋጨፍና፣ በአንዳንድ ቦታዎች ሁለት ሶስተኛው የሚያክለው ህዝብ ማለቅ የሚያመለክተው፣ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ከአፍሪቃ ይልቅ በአውሮፓ  ውስጥ ጭካኔነት የቱን ያህል እንደተስፋፋ ነው። የአንደኛውኛና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተነሱት በአውሮፓ ምድር ነው። እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልክ ስድስት ሚሊዮን የሚያክሉ ይሁዲዎች ያለቁት በአውሮፓ፣ በተለይም በጀርመን ምድር ነው። ከዚህ ስንነሳ ጥቁር መንፈስ የለውም ወይም መንፈሱ የተሰለበ ነው፤ ርህራሄና ሰብአዊነት የለውም፤ እንዲሁም ለኤስቴቲክስና ለፈጠራ ስራዎች የተፈጠረ አይደለም፣ የሚለው አባባል የታሪክን ሂደትና የባህልን ሚና ከቁጥር ውስጥ በማስገባት ሊያገናዝብ ያልቻለ ምርምር ነው። ይሁንና ግን በካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መያዝና በትምህርት መዘበራረቅ የተነሳ አዲሱ የአፍሪቃ ኤሊት ከገንዘብ በስተቀርና የራሱን ኑሮ ከማደላደል በስተቀር ለስልጣኔ ለመቆም እንደማይችል እያረጋገጠ ነው። በብዙ የአፍሪቃ አገሮች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ዕውነትም የጥቁር ኤሊት መንፈሱ የተሰለበ ነው የሚያሰኝበት ሁኔታ ውስጥ የግዴታ እንወድቃለን።

       ወደ ዕውቀትና ስልጣኔም ስንመጣ እንደዚህ በቀላሉ በአፍሪቃ ምሁራን ድክመት ላይ ሊሳበብ የሚችል ጉዳይ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ እራሷ የስልጣኔ አፍላቂ የሆነችው ጥቁር አፍሪቃ ከግሪክ ስልጣኔ ተገልላ እንድትኖር ተገዳለች። ሁለተኛ፣ ግብጽ/አሊክሳንድርያ የተገነባው የዕውቀትና የስልጣኔ መመራመሪያ መጻህፍት ቤት በሮማውያን ይቃጠላል። ቀጥሎሞ በአረቦች ይወድማል። የተቀረው በእንግሊዞችና በፈረንሳዮች ይዘረፋል። ለምሳሌ ጄምስ ዎት አገኘ የተባለው የጭስ ኃይል ማምንጫ ቴክኖሎጂ በአሌክሳንድርያ ተመራማሪዎች ተስሎ እንደነበረና ይህም በእንግሊዞች እንደተሰረቀ ተጽፎ ተቀምጧል። ባጭሩ ግብጽ/ጥቁር አፍሪቃ፣ አሊክሳንድርያ በተቋቋማው ለጥናትና ለምርምር የሚሆን መጻህፍት-ቤት በዚያን ጊዜ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መሰረት የሚሆን መሰረት እንደነበራት ብዙ ጊዜ በሪፖርት መልክ ቀርቧል። ስለሆነም ወደ ዛሬይቱ አፍሪቃ ስንመጣ ያለውን ችግር እንደዚሁ በጥቁርና በነጭ የመሳል ጉዳይ ሳይሆን ለምን አፍሪቃ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን እንዳልቻለች ከብዙ አኳያዎች አንጻር መመልከቱ ችግሩን ለመረዳትና አማራጭ መፍትሄም ለመስጠት ይጠቅመናል።

       ወደ ሌላውና ወደ ታወቀው የታሪክ ጉዳይ ስንመጣ ደግሞ፣ አብዛኛውን ጊዜ በኛ ዘንድ እንደቁም ነገር የማይወሰድ የታሪክ ሂደት አለ። ይኸውም ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በጥቁር አፍሪቃ ላይ የደረሰው ተደጋጋሚ ወረራና ሰዎችን እንደ ከብት ማጋዝ ነው። እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በተለይም እንደ ናይጄሪና ጋና እንዲሁም ቲምቡክቱ የመሳሰሉት በንግድና በዕደ-ጥበብ ሙያ የበለጸጉ  እንደነበር ነው። ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ይካሄድ የነበረው የባሪያ ንግድ  በተለይም አዋቂዎችን፣ የዕደ ጥበብ ሰዎችንና ሊሰሩ የሚችሉ ኃይሎችን ሁሉ እየሟጠጠ ወሰደ። እስከዚያን ጊዜ ድረስ የተመሰረቱት ከተማዎችና የዳበሩ ዕውቀቶች እንዳሉ ወደሙ። የቀሩት ሽማግሌዎችና ህጻናት በዚያው ሊቀጥሉ አልቻሉም። ይህ አፍሪቃን የማደንቆርና የማድኸየት ጉዳይ ደግሞ በዘመነ ቅኝ-ግዛት ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ተጠናከረ። የቅኝ ግዛት አስተዳዳሪዎች የአፍሪቃን ገበሬዎችና የዕደ-ጥበብ አዋቂዎች አውሮፓውያን በሚፈልጉት ሙያ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ አስገደዷቸው። ልዩ ልዩ ሰብሎችን ከማብቀል ፈንታ ወደ ውጭ ለአውሮፓ ኢንዱስትሪ የሚሆን ጥሬ ሀብትና ምግብ ብቻ እንዲያመርቱ ተገደዱ። በዚያውም ወደ ውስጥ የስራ ክፍፍል እንዳይዳብር፣ ከተማዎች እንዳይመሰረቱና ዕውቀት እንዳይስፋፋ የአውሮፓ ቅኝ ገዢ መሪዎች መንገዱን ሁሉ ዘጉ። ብዙ የአፍሪቃ አገሮች በ60ዎቹ ዐመታት ነፃ ወጡ እስከተባለበት ድረስ ለዕድገት የሚሆናቸውን መሰረታዊ እርምጃዎች እንዳይወስዱ ታገዱ። ነፃ ወጡ ከተባሉም በኋላ የድሮው የስራ ክፍፍል በአዲስ መልክ እንዲቀጥል ተደረገ። አፍሪቃ ጥሬ አምራች እንጂ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን የለባትም የሚለው ፈሊጥና ተንኮል በመቀጠል የአፍሪቃን ችግር ውስብስብ አደረገው። አንዳንድ ራሳቸውን ለመቻል የተፍጨረጨሩ እንደጋና የመሳሰሉት አገሮች የመንግስት ግልበጣ እየተደረገባቸው መረጋጋትና ማሰብ እንዳይችሉ ሁኔታው ታጠረባቸው። ለምሳሌ ዩጋንዳ በስድሳዎቹና በሰባዎቹ መጀመሪያ ጥሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የምታሳይና ብዙ የተማረ ኃይልም ነበራት። እንግሊዞችና ሞሳድ አንድ ላይ በመተባበር የዶክተር ሚልተን ኦቦቴን መንግስት በመጣል ደደቡን ኢዲያሚንን ስልጣን ላይ በማውጣት ለብዙ መቶ ሺህ ምሁራን መሞትና መሰቃየት እንዲሁም መሰደድ ምክንያት ሆነ። በዚህም ምክንያት ዩጋንዳ ቀደም ብሎ በተከፈተው የኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ልትጓዝ አልቻለችም። ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለ በኋላ በእንግሊዞች፣ በፈረንሳይ የስለላ ድርጅትና በሲአይኤና በሞሳድ ከሃምሳ በላይ የሚቆጠር የመንግስት ግልበጣ ተደረጎባቸዋል። ቆራጥ መሪዎቻቸው በውስጥ አርበኞች ተገድለውባቸዋል። ስለዚህም ስለ አፍሪቃ የዕውቀት ችግርም ሆነ ስለ ምሁሩ ሚና ስናወራ ከዚህ የታሪክ ሂደት ነጥሎ ለማተት መሞከር ነገሩን በደንብ እንዳንረዳ ያግደናል።

       በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ የተያያዘው በከፍተኛ ደረጃ ለስልጣኔ የሚሆነውን ዕውቀት ማበላሸት ወይም ታዳጊ ምሁራንን ጭንቃላታቸው እንዲጨልም ማድረግ ነው። ኤምፕሪሲዝም የሚባለው የሶፊስቶች የዕውቀት መመሪያ አሸናፊ ሆኖ በመውጣቱ የዓለም ማህበረሰብ ሁሉ እንዲከተለው ተደረገ። ለምሳሌ በታወቁት አሜሪካዊ ፈላስፋና የታሪክ ተመራማሪ በፕሮፌሰር ፓውል ፌየርአበንድ “የተሳሳተው የአርቆ አሳቢነት መንገድ”(The Wrong Road of Rationalism)በሚለው እጅገ ግሩም መጽሀፋቸው ዕውነትን ለመፈለግ የተደረገውን ትግልና አስቸጋሪ ጉዞ በማመልከት፣ በተለይም በ20ኛውና በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ከንፅፅራዊነት ይልቅ ፍጹማዊነት የበላይነትን በመቀዳጀት ብዙ ህዝቦችና አገሮች የተሳሳተውን መንገድ መከተል እንደተገደዱ ነው። በሚያሳምን መንገድ፣ በፕሮፌሰሩም ዕምነት በየትምህርት ቤቱና በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት ትምህርቶች ዕውነተኛውን ዕውቀት እንድንቀስም የሚያደርጉን ሳይሆኑ ለራሳችን ጥቅም ብቻ እንድንፘፘጥ የሚያስገድዱን ናቸው። በመሆኑም የዓለም ማህበረሰብ ችግር፣ ሁሉም በአንድ መድሃኒት ብቻ ነው ሊፈወስ የሚችለው በሚል ዕምነት ዓለም-አቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ተደረገ። የየአገሮች የባህል፣ የታሪክ፣ የህብረተሰብና የፖለቲካ አወቃቀሮች ከዕውነተኛ ዕወቀት ተነጥለው በመታየታቸው ብዙ የአፍሪቃ ምሁራን፣ እኛንም ጨምሮ ማንነታችንና በየአገሮቻችን ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች ለማወቅም ሆነ ጠቀሜታቸውን ለመረዳት የማንችልበት ሁኔታ ተፈጠረ። ለምሳሌ ብዙዎቻችን በአገራችን ምን ምን የዛፍ ዐይነቶች እንደሚበቅሉና ለምንስ ጥቅም እንደሚውሉ የሚያውቀው ምሁር ነኝ ባይ በጣት የሚቆጠር ነው። በተለይ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ ያደገ በአገሩ ውስጥ ምን ምን ዐይነት ፍራ-ፍሬዎች እንደሚበቅሉና ለጥቅም እንደሚውሉ የሚያወቅ የለም ማለት ይቻላል። የዶቅማንና የእንጆሪን ወይም የአውጥን ፍራ-ፍሬዎች የሚያወቅ እስካሁን አላገኘሁም። አገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች የተቋቋሙትም መንግስታት በምዕራቦች ድጋፍ ስለሆነ ተግባራቸው ሁሉ ባህላዊ ተሃድሶ እንዳይኖርና ዕውቀት እንዳይስፋፋ ማድረግ ነው። የወጣቱ ትውልድ ከባህሉና ከታሪኩ ጋር እንዲተዋወቅ በማድረግ በምን ዕይነት መልክ ለስልጣኔ መታገል እንዳለበት የሚያበረታቱ አይደሉም። ለምሳሌ የብዙ አፍሪቃ አገሮችን የኢኮኖሚ ዕደገትን ሁኔታ ስንመለከት፣ ከዚህ ከተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕውቀት የተያያዘ መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። በዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው ድንጋጌ ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎች ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትን ፈጣሪና የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በማያያዝ ትርፋማ ምርት ለማምረት የማይችሉት፣  ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት የሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ተነጣጥለው ስለሚታዩና፣ ትምህርቱ ከዕውነተኛ ዕውቀትና ስልጣኔ ውጭ የተነደፈ በመሆኑ ነው። የከተማዎች በዕቅድ አለመሰራት፣ በገጠርና በከተማ ስለሚኖረው ግኑኝነት በቅጡ አለማሰብ፣ በተወሰኑ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ብቻ በመረባረብ የጥሬ ሀብትና የሰው ጉልበት እንዲባክን ማድረግ፣ ውስጣዊ ሀብትን ሊፈጥሩ የማይችሉ የተዝረከረኩ የንግድ ተግባሮች መስፋፋት…ወዘተ. የሚያመለክተው በስልጣን ላይ ያሉት መሪዎችም ሆኑ ምሁራኑ በጥልቀትና በስፋት እንዳያስቡ ከመጀመሪያውኑ ጭንቅላታቸው ስለተጋረደ ነው። ስልትና ትንተናዊ አስተሳሰብ(Methodology and Analytical Thinking) በብዙ የአፍሪቃ አገሮች እንደሳይንሳዊ መመሪያና መመራመሪያ ዘዴዎች ተደርገው ስለማይወሰዱ የሚሰሩት ስራዎች በሙሉ የመጨረሻ መጨረሻ ህብረተሰብአዊ ውጤትን የሚሰጡ አይደሉም። ለምሳሌ በብዙ የምዕራብ አውሮፖ አገሮች የከተማ አገነባቦች ተመሳሳይነት ሲኖራቸው፣ ወደ አፍሪቃ ስንሄድ በብዙ አገሮች ተመሳሳይነት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። የተዝረከረኩ፣ የኮስሞስን ህግ ያልተከተሉና የሰውን አስተሳሰብ የሚያዘበራርቁ ሆነው፣ የሰው ልጅ ተግባር በዚህች ዓለም ላይ ሲኖር ምን ማድረግ እንዳለበት መንገዱን ሁሉ የዘጉበት ናቸው።

       ቀጠል ብለንም ስንመረምር፣ ከፖለቲካ ነፃነት በኋላ በየአገሮች የተዋቀረውና ተግባራዊ የሆነው ትምህርት አዲሱን ትውልድ አርቅቆና አርቆ-አሳቢ፣ በስልትና በሰፊው፣ እንዲያስብ አላደረገውም። የትምህርቱ አሰጣጥ እያንዳንዱ ወጣት፣ ራሱን አውቆ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን ተረካቢ መሆኑን የሚያስገነዝበው አይደለም። ታታሪነት፣ በዲሲፕሊን መስራትና በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥኖ አገርን በጋራ መገንባት የሚለው የተቀደሰ መንፈስ ከመጀመሪያውኑ በትምህርት መስክ የሚሰጥና የሚሰበክ አልነበረም፤ አይደለምም። ትምህርቱም በቀጥታ ወደ ተግባር የሚመነዘርና ለጠቅላላው ህብረተሰብ ሀብት ሊፈጥር በሚችል መልክ የተዘጋጀ አይደለም። ወደ ውጭ ለከፍተኛ ትምህርት የሚወጣው ደግሞ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ አገሩ ሲመለስ ተቀጥሮ የሚሰራባቸው መስሪያቤቶች ለፈጠራ ስራ የማያመቹ ብቻ ሳይሆኑ የሰውን ሞራል በመግደል ታሽቶ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው። ለምሳሌ ፊዚክስ ወይም ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ወይም ሌላ ሌላ ነገር ተምሮ የመጣ የተማረውን ትምህርት ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችልባቸው ላቦራቶሪዎችና ኢንስቲቱሽኖች ተዘጋጀተው አይጠብቁትም። እንዲሁም፣ ስለ አውሮፕላን ወይም መኪና አሰራር የተማረ ሰው ወደ አገሩ ሲመለስ የግዴታ አውሮፕላንም ሆነ መኪና መስራት ባይኖርበትም-ቴክኖሎጂው ስለሌለና ኢኮኖሚው ስለማይፈቅድ-ሙያውን በሌላ መልክ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችልበትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ሊፈጥር ያሚያስችሉት መሳሪያዎችና የምርምር ጣቢያዎች አይገኙም። ስለሆነም አስፈላጊ ኢንስቲቱሽናዊ ተቋሞች በሌሉቡት አገር ውስጥ የተማረው ባለሙያ ዕውቀቱ ባክኖ ይቀራል ማለት ነው። ከዚህ በተረፈ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካ የሚማሩ ምሁራን የተለያየ አስተሳሰብ ለምደው ይመጣሉ። አዳዲስ አስተሳሰብን መቅሰሙ ክፋት ባይኖረውም፣ አሜሪካ የተማረው አውሮፓ ውስጥ የተማረውን ወደ መናቅ ይደርሳል። ስለሆነም በተለያየ ሙያ ሰልጥነው የመጡ ምሁራን ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ መንፈሳዊ አንድነት ሊመሰርቱ አይችሉም። ለምሳሌ የአውሮፓውን የዕውቀትና የዕድገት ታሪክ ስንመለከት ከሶስት ሺህ ዐመት ጀምሮ ሬናሳንስ አቆራርጦ እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በሁሉም ምሁራን ዘንድ የአስተሳሰብ ግኑኝነት እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት ይደረግ ነበር። በምቀኝነት ወይም በአውቅሁኝ ባይነት አንደኛው ሌላውን ለማጥፋት የሚዘጋጅ ሳይሆን፣ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው አንድ ላይ በመሰባሰብ፣ በማጥናትና በመወያየት ለአገር የሚያገለግለውን ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት መንደፍ ነበር። እንደዚህ ዐይነቱ የአሰራር ስልት በሌሎች የአፍሪቃ አገሮችም ሆነ በኢትዮጵያችን የተለመደ አይደለም። በኢትዮጵያችን አብዛኛው ምሁር ሀሳብ የማፍለቅ ልምድ ስለሌለው ጊዜውን በሆነው ባልሆነው ሁኔታ ያጠፋል። በዚህም ምክንያት በብዙ የአፍሪቃ አገሮች ዕውነተኛ የብሄራዊ ስሜት ሊዳብር አልቻለም። ብዙ የአፍሪቃ ምሁራንም፣ እኛንም ጨምሮ፣ አገር፣ ህብረተሰብና ብሄራዊ-ነፃነት እንዲሁም ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ምን ዐይነት ትርጉም እንዳላቸውና፣ ደረጃ በደረጃም ምን ምን ነገር መካሄድ እንዳለበት እምብዛም ከሰውነቻን ጋር የተዋሃዱ አይደሉም።

       ስለሆነም ስለ አፍሪቃ ምሁራን የአስተዋጽኦ ድክመትም ሆነ ኋላ-ቀርነት ስናወራ እንዲሁ በደፈናው ዲሞክራሲ ስለሌለ ነው፣ አምባገነኖች ስለሆኑና የህግ- የበላይነት ባለመኖሩ ነው ብለን በአጭሩ የምናስቀምጥ ከሆነ ለተወሳሰበው ችግር ፍቱን መፍትሄ ማቅረብ አንችልም። በሌላ ወገንም ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ አላቸው፤ በየጊዜውም ምርጫ ሲካሄድ ፕሬዚዳንቶችና አስተዳደሩ ካለምንም ችግር ስልጣን ያስረክባሉ የሚለው የተስፋፋ አባባል ችግሩን ለመረዳት አያስችለንም። ለምሳሌ በብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የሚወደሰውን የጋናን ፖለቲካ አወቃቃርና ኢኮኖሚ ሁኔታ ለተመለከተ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች እሰከዚህም ተሽሎ የሚገኝ አይደለም። ስለ ጋና የፖለቲካ ሁኔታ የሚጽፉ ምሁራን ጋና ያልነበሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚካሄደውን ሁኔታ የማያውቁ ናቸው። 1ኛ) የጋና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አብዛኛውን በካካዎ ላይ የተመሰረተ ነው። የወርቅ ማዕድኑን የአንግሎ-ካናዲያን ማዕድን አውጭ ኩባንያ የሚቆጣጠረው ሲሆን፣ ለመንግስት የሚገባው ገቢ ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚያደርገው አስተዋጽዎ ቁጥር ውስጥ የሚገባ አይደለም። 2ኛ) ጋና በሰማንያኛው 㗹ዓመተ ምህረት መጀመሪያ ላይ የዓለም ባንክንና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን የመዋቅር ማሰተካከያ(Structural Adjustment Program) የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረገችና እንደምሳሌ የምትወሰድ መጫወቻ ልጅ ነች እየተባለ የሚቀለድባት አገር ነች። በመሆኑም በፖሊሲው መሰረታዊ ለውጥ አለማምጣት የተነሳ፣ የጋና የውጭ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ተደረገ። በሌላ አነጋገር፣ ወደ ውጭ ከምትልከው ይልቅ ወደ ውስጥ የምታስገባው በጣም ከፍ ያለ ነበር። በተጨማሪም በዕዳ መተብተብና የወለድ ወለድ ከፋይ እንድትሆን ተገደደች። 3ኛ)ወደ ውስጥ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም መለመዱ ብቻ ሳይሆን፣ በሀብታምና በደሀ መሀከል ያለው የገቢ ልዩነት በጣም እየሰፋ በመምጣት ህብረተሰብአዊ መዛባትን ፈጠረ። 4ኛ)ገበያው ለውጭ ምርት ልቅ በመሆኑ ቆሻሻ ማራገፊያ ሆነ። እዚህ አውሮፓ ውስጥ ለምግብ የማይሆኑ የበሬ፣ ዶሮና የአሳማ ትርፍራፈዎች ገበያ ላይ ይሸጣሉ። 5ኛ) እንደዚሁ አካባቢን የሚያቆሽሹና ጤንነትን የሚያቃውሱ የኤሌክትሮኒክስ ትራፊዎች ከአውሮፓና አሜሪካ እየተራገፉ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ እየፈጠሩና ወጣቱም ኑሮውን ለማሸነፍ ሲል እነዚህን ቆሻሻዎች እየለቀመ ራሱን የሚያስተዳድር ነው። 6ኛ) ከራውል በኋላ ስልጣን ላይ የወጣው ኮርፉ የዓለም ባንክ መጥጦ መጥጦ ከጨረሰው በኋላ እንደገና ደግሞ የአሜሪካንን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ የመመረጥ ዕድል ያገኘ ነው። ታዲያ ምኑ ላይ ነው ስለ ጋና ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ የሚወራው? ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ከኑሮ ሁኔታ መሻሻል ውጭ ተነጥሎ የሚታይ ከሆነ ስለ ዲሞክራሲ ያለን ግንዛቤ በጣም የተበላሸ ነው ማለት ነው። ወይም ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እዚያ ድረስ ሄዶ ፓርሊያሜንት ውስጥ ንግግር ስላደረገና ስለ ጋና መልካም አስተዳደር ስላወደሰ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ብለን የሚያዛናናንና የጋናን ዐይነት ዲሞክራሲ የምንመኝበት ምክንያት የለም። ፕሬዚደንት ኦባማ ስለ አፍሪቃ ብቻ ሳይሆን ለሌላው የዓለም ህዝብም ያለው አመለካከት የቀና ቢሆንም፣ ከአሜሪካ የጠቅላላው ፖሊሲ ጥቅም ውጭ የሚያደርገው አንዳችም ነገር የለም። ስለዚህም ስለ ዲሞክራሲ በምናወራበት ጊዜ ከዕውነተኛ ዕውቀት መዳበርና ከአጠቃላይ ስልጣኔ ውጭ ነጥለን በፍጹም ማየት የለብንም።

ዕውነትን መፈለግና የባህል ጉዳይ!

           አብዛኛውን ጊዜ በእኛ ኢትዮጵያውኖች ዘንድ ስለባህል ሲወራ፣ ባልሳሳት የባህልን ትርጉም እጅግ በጠባቡ ነው የምንተረጉመው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ አላት፤ የኢትዮጵያ ባህል የተለየ ነው፤ እያልን የኛን ልዩነት ለማውራት እንሞክራልን። በመጀመሪያ ደረጃ ታሪክም ሆነ ባህል በአንድ ቦታ ላይ የቆሙ(Static)  አይደሉም። ተነጣጥለው እስካልታዩ ድረስ ታሪክም ሆነ ባህል ውሰጠ-ኃይላዊ ክንውኖች(Dynamic Processes)ናቸው። ራሳቸውንና የራሳቸውን ሁኔታ ሊለውጡና ታሪክም ሊሰሩ የማይችሉ እንስሳዎች ብቻ ናቸው።

       ስለባህል ስናወራ፣ የሰው ልጅ ባህላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ምግባራዊና ጥበባዊ ነው። እነዚህ ነገሮች አንድ ላይ የሚጓዙ እንጂ፣ አንደኛው ከሌላው ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የሰው ልጅ የተፈጠረው ስልጣኔዎች በሙሉ በአንዳች ኃይል ተዘጋጅተው ከተጠናቀቁ በኋላ ነው ብለን ካልገመትን በስተቀር፣ በዚህች ዓለም ላይ ሲወረወር ራሱን ለማዳን ሲል የግዴታ በአደንና ፍራፍሬ እየለቀመ ይኖር ነበር። ለማደንም ሆነ ፍራ ፍሬዎችን ለመልቀምና ለመጠቀም ይጠቀምባቸው የነበረው መሳሪያዎች ዲንጋይን በመቅረጽና በማሾል ነበር። ይሁንና ግን በዚህ ሳይረካ አንድ ላይ በመሰባሰብና ተቀማጭ በመሆን ከብትን ማርባትና የእርሻ ተግባርን ማካሄድ ጀመረ። ይህ ተቀማጭነትና፣ በመንደርና በከተማዎች መከፋፈልና በልዩ ልዩ ሙያዎች መሰልጠን የግዴታ በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ የንግድ ልውውጥ እንዲካሄድ መንገዱን ከፈተ። ከህብረተሰባዊ የባህል ግምገማ (Socio-Cultural Studies) አንጻር ይህ ዐይነቱ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ የባህል ዕድገት ምልክት ነው። ባህል የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ውጤት እንደመሆኑ መጠን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች እንደ የአካባቢያቸው ሁኔታ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የባህል ዕድገታቸው ልዩ ልዩ መልክና የህብረተሰብ አወቃቀር ይዞ ሊሄድ ችሏል። የዓለም ማህበረሰቦች በሙሉ አንድ ዐይነት ጉዞን አልተጓዙም። በዓለም ላይ ያሉ ህብረተሰቦች በሙሉ የተለያዩ ህብረተሰብአዊ ስርዓቶች በመመስረት፣ አንደኛው ከሌላኛው ሳያውቁም ሆነ አውቀው በመለያየት የተለየ ስርዓትን መስርተዋል። በተለይም የስታሊንን የታሪክ ግምገማ የተከተሉ የማርክሲስት ጸሀፊዎች በዓለም ላይ ያሉ ማህበረሰቦች በቀጥታ ከታች ወደ ላይ(Linear)  ተመሳሳይ በሆነ የማህበረሰብ አደረጃጀት ተጉዘዋል የሚለው ከዕውነተኛው የታሪክና የባህል ሂደት ተነጥሎ የተጻፈ አሳሳች አቀራረብ ነው። በሌኒንና በስታሊን የዳበረው የማርክሲዝም ቲዎሪ በ60ሳዎቹና በ70ዎቹ ዐመታት ልክ እንደዛሬው ዐይነት የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ብዙ የሶስተኛው ዓለም ምሁራንን ሊያሳስት ችሏል። በተጨማሪም የስታሊንና የሌሎች የምስራቅ አውሮፓ አገሮች የማርክሲዝምን አተረጓጎም ወደ ተግባር ሲመነዘር ህብረተሰቦቻቸውን በአንድ ወጥ ባህል እንዲቀርጹ አስገድዷቸዋል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የወዝአደሩን ባህል(Proletarian Culture) መከተልና ከሰውነቻው ጋር ማዋሃድ አለባቸው። የህንጻ አሰራሮችም ጥበባዊ መሆናቸው ቀርቶ አንድ ወጥ መሆን አለባቸው። የሶሻሊዝም ሬያሊዝም(Socialist Realism) በሁሉም ቦታ ተግባራዊ መሆን አለበት። በሙዚቃም፣ እንደክላሲካል ዐይነቱ ሙዚቃ፣ በተለይም የቬቶበን ሙዚቃ በአንዳንድ አገሮች ክልክል ነው። ምክንያቱም መንፈስን የማለዘብ ኃይል ስላለውና ከበርቴያዊ ባህርይን ስለሚያስተላልፍ ነው። ይህንን የመሰለ አተረጓጎም የየግለሰቦችን የፈጠራ ስራ ማፈን እንደቻለ የማይታበል ሀቅ ነው። የኒዎ-ሊበራሊዝምም ርዕዮተ ዓለም ነጻ ንግድን ተገን በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምና ባህልን እያስፋፋና ከውስጥ የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገር ህዝቦችን ኑሮ እያናጋ ነው። ህብረተሰቦች በገበያ ሎጂክ መደራጀት አለባቸው እየተባለ ወደ ተወሰነ የአስተራረስ ስልት እንዲያመሩ በማስገደድና በተወሰኑ በገበያ ላይ ሊሸጡ በሚችሉ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ በማድረግ ለህብረተሰብ የሚጠቅሙ የተለያዩ ሰብሎች እንዲወድሙ ይደረጋሉ። የፍጆታ አጠቃቀምም እንደየአገሩ ሁኔታና ባህል መሆኑ ቀርቶ በብዙ አገሮች ተመሳሳይ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ አንድ ወጥ የአሰራር ስልትና አመጋገብ ደግሞ የማሰብና የመፍጠር ኃይልን ያፍናል። የተፈጥሮን ህግ የሚፃረር በመሆኑ፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ጤንነት ላይ መቃወስን ያስከትላል። ምክንያቱም ተፈጥሮ ሚዛናዊ በሆነ መልክ ተግባፘን ልትፈጽም የምትችለው የተለያዩ ነገሮች ተቀነባብረው ወይም ጎን ለጎን ሲኖሩ ብቻ ነው። በተጨማሪም፣ በመስታወት የተሸፈነ የህንጻ አሰራር፣ ከአየሩ ጋር የማይስማሙና ጥበብ የሌላቸው ራዣዥም ፎቆች የሰውን ኑሮ እያዘበራረቁና ራሱን በራሱ እንዳያገኝ መንገዱን እየዘጉበት ነው። ለምሳሌ በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የሚሰሩ በመሰታወት የተሸፉኑ ባለ ሃያ ወይም ከዚያ በላይ ፎቆች ከኢኮኖሚም ሆነ ከሙቀት እንዲሁም ከጽዳት አንጻር ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል። በመስታወት የተሸፈነን ባለ 20 ፎቅ ቤት በየጊዜው ለማጽዳት ብዙ ወጪ ማስፈለጉ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዐይነቱን ፎቅ በተራ መሰላል ማጽዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሁለተኛ፣ መስታወቱ ከውጭ ስለሚመጣ ወደ ውስጥ ለዕድገት ሊጠቅም አይችልም። ኢኮኖሚው ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀትን የማያሳይ ከሆነ ደግሞ ከረዥም ጊዜ አንጻር እንደዚህ ዐይነቱን ህንጻ ለመጠገንና ለማደስ በጣም ያስቸግራል። ያም ሆነ ይህ፣ የሶሻሊዝሙ አብዛኛውን ጊዜ በጉልበት ላይ የሚመካ ሲሆን፣ የኒዎ-ሊበራሊዝም የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ግን ማር ቀብቶ በማታለል ነው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ባህላዊና ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን የሚፈጥረው።

       ስለሆነም ስለባህል በምናወራበት ወቅት የሰው ልጅ እንደ የአካባቢውና በላዩም ላይ ቁብ ባሉት አገዛዞች በመመራት ዕውነትን ለመፈለግና የኑሮን ትርጉም ለመረዳት በሚያደርገው ጥረት እንደ የአካባቢዎች የተፈጥሮ ሁኔታ የተለያዩ ባህሎችን መስርቷል። ይሁንና ሁሉም ማህበረሰብ ደግሞ እንደ አጀማመሩና ጥረቱ በዚያው ሊቀጥል አልቻለም። ራሱ በፈጠራቸው አስተሳሰቦች፣ ባህሎችና ልምዶች በመታወር በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ ተመሳሳይ ባህሎች ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ በመሸጋገር የሰው ልጅ ኑሮ እዚያው በዚያው እንዲቀር ተገዷል። በሌላ ወገን ግን ህብረተሰብአቸውን ከውጭ ለመጣ አዲስ ባህል ክፍት ያደረጉ ማህበረ-ሰቦች የግዴታ ከአዲሱ ባህልና የአኗኗር ስልት ጋር በመጋጨት አዲስ ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ላለ ባህል መንገድ ሊከፍቱ ችለዋል። በአንፃሩ ግን አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በራቸውን የዘጉ ማህበረ-ሰቦች እዚያው በዚያው በመንደፋደፍ ለዕድገት የሚሆናቸውን መንገድ መቀየስ አልቻሉም። አንዳንድ ማህበረ-ሰቦች በድሮው ታሪካቸው በመዝናናት ብቻ በአረጀ ባህል በመታሰር ጭንቅላታቸውን ለስልጣኔ እንዳይከፍቱ ታገዱ። ለምሳሌ ይህንን አጥብቆ የተረዳው ላይብኒዝ በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን  የተካሄደውን የርስ በርስ መጨፋጨፍ ምክንያት ካጠና በኋላ፣ አውሮፓን ለማዳን በአውሮፓ ምሁራን ዘንድ የአስተሳሰብ አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ ትግል ያደርግ ነበር። በተለይም ከስዊድን ፈላስፋዎች ይደርስ የነበረው መልስ፣ እኛ ታሪክ የነበረን ሰዎችና ከማንም የምንበልጥ ነን እያሉ ነበር የሚጽናኑበት። ላይብኒዝም ይህንን ትክክለኛ ያልሆነ አባባል በማስረዳት፣ ስላለፈው ታሪክ ሳይሆን መዝናናት ያለብን፣ ዛሬ ያለንበትን በመገንዘብ በአዲስ መንፈስ ተነሳስተን ለሚቀጥለው ትውልድ ምን ዐይነት የታሪክ መሰረት ጥለንለት ማለፍ እንችላለን ብለን ነው ራሳችንን መጠየቅ ያለብን እያለ የሚመክራቸውና የሚያሳስባቸው።

        ከዚህ ስንነሳ በአንድ የተወሰነ ወቅት ራስን ለማሸነፍ የተደረገው ጥረት በዚያው ሊቀር የተገደደውና የድሮው ባህል አማራጭ የሌለው ተደርጎ የሚወሰደው በተጨማሪም ከውስጥ ሊፈልቅ የሚችል አዲስ አስተሳሰብ ሊፈጠር ሳይችልም ሲቀር ነው። ቢፈጠረም እንኳ አዳዲስ አስተሳሰቦች እንደመጥፎ ተግባር ወይም ስርዓቱን የሚቀናቀኑ ተደርገው ስለሚቆጠሩ ወዲያው ደብዛቸው እንዲጠፋ ይደረጋል። አንድ ውድ ወንድሜ የመጀመሪያውን የዚህን ክፍል ጽሁፍ ካቀርብኩ በኋላ ከኢትዮጵያ ባህል ጋር የበለጠ እንደተዋወቅ፣ በተለይም ከአስራሁለተኛው ክፍለ-ዘመን አንስቶ እስከ አስራ- አምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የነበረውን የሃሳብ መለያየትና በአንዳንድ አካባቢዎችም “ዕድገትን ለማምጣት” የተደረገውን ጥረት በቀጥታ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተጻፈና በዚያን ጊዜ ተደርሶ በአንድ ግለሰብ በብዙ ጥረት የተተረጎመውን ለመላክ ጥያቄ አቀርበልኝ። እኔም ዝግጁ መሆኔን ካሳወቅሁት በኋላ ከአራት ሳምንታት በኋላ ቀጥታ ከኢትዮጵያ ይልክልኛል። መጽሀፉን አገላብጬ ስመለከተው በጥሩ አማርኛ የተቀነባበረ ብቻ ሳይሆን፣ በዚያን ጊዜ የነበረውን ትግል፣ የብዙ ቤተ-ክርስቲያናትንና ገዳሞች ስራዎች የሚያትት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ቦታዎች ለዕድገትና ለባህል ለውጥ የተደረገውን ጥረት የሚጠቁም ነው። በአብዛኛው ግን ካህናቱ ቤተ-ክርስቲያናትንና ገዳማትን መስራትና ለማስፋፋት ሲጠመዱ፣ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ደግሞ በአገዛዞችም ሆነ በአንዳንድ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አክራሪ መሪዎች ህይወታቸው እንደሚቀጭ የሚያመለክት ነው። መጽሀፉ እንደሚያረጋግጠው፣ የራሳቸው ጥቅምና ስልጣን የሚነካባቸው ወይም የሚቀነስባቸው የሚመስላቸው ካህናት መጽሀፍ ቅዱስን እነሱ በሚረዱት መልክ ሲያስተምሩና ብዙ ተከታዮችም ሲያገኙ ትምህርቱን በማጣመምና ለነገስታቱ የማይሆን ነገር በማውራት ቀና አስተሳሰብ ባላቸው ቀሳውስት ላይ ተንኮል በመሽረብና በማስጠመድ እንዲደበደቡና አካባቢውን ጥለው እንዲሄዱ ያደርጉ ነበር። ይህ ተንኮል እየተደጋገመ በመሄዱም በአንዳንድ ቦታዎች የተጀመሩ ጥሩ ስራዎች እንዲወድሙና በአካባቢውም ዕድገት እንዳይኖር እንቅፋት ለመሆን በቅቷል። መጽሀፉ፣ ከአስራሁለተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ብዙ ህዝብና ካህናት በበሽታ፣ በረሃብና በውሃ ጥማት ችግር እርግፍ እያሉ ያልቁ እንደነበርና በዚያን ጊዜ የነበረው ሁኔታ የቱን ያህል አሰቃቂ እንደነበር ያትታል። ይህም ሁኔታ በአውሮፓ ውስጥ የግሪኩና ከዚያም በኋላ የሮማውያኑ ስልጣኔ ከወደመ በኋላና በብዙ የአውሮፓ አገሮች የፊዩዳሉ አገዛዝ ከሰፈነና የካቶሊክ ሃይማኖት የሰውን አስተሳሰብ አፍኖ ከያዘ ጀምሮ፣ በህዝብ ላይ ይደርስ የነበረውን በደልና አሰቃቂ ኑሮና ዕልቂት ያስታውሰናል። በመጀመሪያው ጽሁፌ ላይ ለማተት እንደሞከርኩት፣ ፊዩዳሊዝምም ሆነ የካቶሊክ ሃይማኖት የመጨረሻ መጨረሻ ሊዳከሙና የበላይነትን ሊያጡ የበቁት የግሪክ ስልጣኔ በአረቦችና በመጠኑም ቢሆን በይሁዲዎች አማካይነት ከግሪክ ወደ አረብኛ ከዚያም በኋላ ወደ ላቲን ከተተረጎመ ወዲህ ነው። በአንፃሩ ግን ከግሪኩ ስልጣኔ ጋር መተዋወቅ ያልቻለው የኢትዮጵያ ህብረተ-ሰብ እዚያው ባለበት እንዲቀር ተገዷል። ከቦታ ቦታ የተለያየ አመለካከት የአኗኗር ስልት ቢኖርም፣ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት የፊዩዳሉ ስርዓትና የኦርቶዶከስ ሃይማኖት ህዝቡን የሙጥኝ ብለው በመያዝ ለዕድገት ተቀናቃኝ መሆን ችለዋል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

       በአጠቃላይ ስለባህል ስናወራ፣ ብዙ ነገሮች ተጣምረው እንደሚሄዱና ባህሎችም የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ውጤቶች መሆናቸውን ነው። ስለባህል ስናወራ ስለ ሃይማኖት ብቻና ሰውን በማክበር የሚወሰን አይደለም። የባህል ዕድገት በቆንጆ የከተማ ግንባታዎችና በጥሩ አርክቴክቶች የሚገለጽ ነው። ባህል በሙዚቃ፣ የሰውን አስተሳሰብ ክፍት በሚያደርጉ በጥሩ ስነ-ጸሁፎች የሚገለጽ ነው። ድራማ፣ ቀልድና ቲአትር እንዲሁም ስፖርት ባህላዊ ድርጊቶች ናቸው። እነዚህ እያበቡ ሲሄዱ ደግሞ የሰው ልጅ አስተሳሰብ የበለጠ ሁለንታዊና ጠለቅ እያለ ሲመጣ የተፈጥሮን ትርጉም የመረዳት ኃይሉ ከፍ ይላል። ተፈጥሮን ሲረዳ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚሆነውን መሰረት ይጥላል። አስተሳሰቡ ክልላዊ ወይም በብሄረ-ሰብ የሚወሰን መሆኑ ቀርቶ፣ ብሄራዊ ባህርይ ይይዛል። ብሄረ-ሰቡ ካነቀው ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ሲላቀቅና እሱን እየበጣጠሰ ሲመጣ፣ በራሱ ጥረት ብቻ ኑሮን ማሸነፍ እንደሚችል ይገነዘባል። የተተበተበትን የብሄረ-ሰብ ሰንሰለት ሲበጣጥስና ከሌላው ብሄረ-ሰብ ጋር ሲጋባ የማሰብ አድማሱ ከፍ ይላል። የባህል ተገዢ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ ዕውነተኛ ባህል ታዳጊና በአገር ደረጃ የሚገለጽ፣ እንዲሁም ሁሉንም የሚያስተሳስር መሆኑን ይበልጥ ይረዳል። ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ አገር፣ ህብረተሰብና ብሄራዊ ነፃነት እንዲሁም ግለሰብአዊ ነፃነት የዕውነተኛ ኑሮው መገልጫ ይሆናሉ። ለምሳሌ የአውሮፓን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ሁኔታ ስንመለከት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከማደጋቸውና የሰውንም ህይወት ከመደንገጋቸው በፊት የከተማና የቤተክርስቲያናት ግንባታ ነው የተስፋፋው። ከአስራሁለተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተካሄደው የከተማዎችና የሚያማምሩ የቤተ-ክረስቲያናት ግንባታዎች የሚያረጋግጡት፣ ከባህላዊ የአኗኗር ለውጥ በፊት ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ብቻ የሚደረገው ትግል የትም እንደማያደርስ ነው። ስለዚህም ስለዕውነቱ ነገር ፍለጋ ስናወራ ከሰው ልጅ የመንፈሳዊና የባህል ተሃድሶ፣ ይህም የባህል ተሃድሶ በተግባር ከሚታዩ እንቅስቃሴዎች ውጭ ተነጥሎ ሊታይ በፍጹም እንደማይችል ነው። ይህንን ባጭሩም ቢሆን ከተመለከትን በኋላ ነገሩን የበለጠ ለመገንዘብ በግሪክ ምድር ለአርቆ-ማሰብና ለስልጣኔ አነሳስ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በመጠኑም ቢሆን እንቃኝ። ይህም ሀታታ ዕውነትን መፈለግ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዳን ይመስለኛል።

ከአምልኮአዊ ወደ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ!

        አብዛኛውን ጊዜ ስለግሪክ ስልጣኔ ሲወራ አንዳንዶች ከጠቁር አፍሪቃ የወረሱት ወይም የሰረቁት ነው ይላሉ። ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ ባይሆንም፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ የተጀመረ ስልጣኔ እዚያው አይቆይም፤ ወይም እዚያው ስልጣኔው ዳብሮ ህብረተሰብአዊ ዕምርታን አያመጣም። በእርግጥ ታለስ፣ ፕይታጎራስ፣ ሶሎንና ፕላቶን የመጀመሪያውን ዕውቀታቸውን ግብጽ አገር እንደቀሰሙ እነሱም አይክዱም። ቁም ነገሩ የነሱ ዕውቀትን “የመስረቁ” ጉዳይ ሳይሆን በጥበቡ ምን ሰሩበት ነው። አዳበሩት ወይስ አላዳበሩትም ነው ጥያቄው። ስለሆነም ፍለጋችን በኮረጁት ዕውቀት አማካይነት እንዴት ከአምልኮታዊ አስተሳሰብ ወደ አርቆ-አሳቢነትና(Rational Thinking) የሳይንሳዊ ምርምር ለመምጣት ቻሉ ነው። ይህንን ሳይረዱ የችኮለ ክስ መሰንዘር አመክንዮ ዕድገቱን(Logical Process) መረዳት አይቻልም። ከዚህ ስንነሳ የኛ ፍለጋና ጥያቄ በአንድ የተወሰነ አካባቢ ከብዙ ሺህ ዐመታት በፊት የሚኖርን ህዝብ ከአምልኮ አስተሳሰብ ተላቆ ወደ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እንዲሸጋገር ምን አስገደደው ነው? ይህ ጥያቄ በመጀመሪያው ጽሁፌ ላይ ያመለከትኩትን፣ በተለያዩ አምልኮዎች ማምለክና በፋንታዚ ዓለም ውስጥ መገኘት ምናልባትም ለአርቆ አስተዋይነት አስተሳሰብና፣ እንዲያም ሲል ለሳይንስ ምርምር መንገድ የከፈተ መሆኑን ብዙ መጽሀፎች ካገላበጥኩኝና ካወዳደርኩ በኋላ የደረስኩበት ድምደማን እንደገና ያጠናከረልኝን ሁኔታ ማግኘት ችያለሁ።

       የሆሜር ኤልያስና ኦዴይሴ ግጥሞችና የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ700ዎቹ ዐመታት ገደማ የተደረሱ ሲሆኑ፣ በአፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈውን የጥንት ታሪክና የስልጣኔ ትዝታ የተመረኮዙ ናቸው። በግሪክ በተለያዩ ደሴቶች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1300 ዓ.ም ገደማ ትልቅ ስልጣኔ እንደነበረና፣ ስልጣኔውም የእርስ በርስ ጦርነት እንደፈራረሰና፣ የስልጣኔውም መፈራረስ በጊዜው የነበረውን የመንፈስ አወቃቀርና ህገ-አልባ አገዛዝ ይጠቁማል። ሁለቱም ድርሰቶች በአቀራረብና በጊዜ አጠነቃቀር ሲለያዩ፣ በኤልያስ ድርሰት ውስጥ የአምላኮች ፍጹማዊ ድርጊት ጎልቶ ሲታይ፣ በኦዴይሴው አቀራረብ ግን የግሪክ ህዝቦች ቀስ በቀስ ራሳቸውን ወደ መገንዘብ እየተቃረቡ እንደመጡ ያመለክታል።

       ይሁንና በሆሜርም ሆነ በሆይሶድ ግጥሞች ጎልቶ የሚታየው በጊዜው የግሪክ ህዝቦችን ያልበሰለ አስተሳሰብና፣ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በራሳቸው ሳይሆን በአምላኮች ይደነገግ እንደነበር ነው የሚታመነው። እነዚህ የተለያየ ስም ያላቸው አምላኮችም የተለያየ ባህርይ እንደነበራቸውና ከላይ ወደ ታች የሆነ አገዛዝ የሚመስል፣ አንደኛው አምላክ ከሌላው የበለጠና ሃሳባቸው በየጊዜው እንደሁኔታው እንደሚለዋወጥ የሚጠቁም ነው። ስለሆነም በመሬት ላይ የሚከሰት ማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ፣ ለምሳሌ የውሃ ሙላትና የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እንዲሁም ደግሞ ነጎድጓድና መብረቅ በአምላኮች የሚላኩ የሰውን ልጅ መቅጫ መሳሪዎች እንደነበሩ ይታመን ነበር። ሁሉም መጥፎ ነገር በእነዚህ አምላኮች ቁጥጥር ስር የነበረና ደስ ሲላቸው ጥሩ ነገር የሚያደርጉ፣ የሚያስቀይማቸው ነገር ደግሞ ካለ አደጋዎች በመላክ የሰውን ልጅ ይቀጡም እንደነበር የታመነ ነገር ነው። በሆሜርም ሆነ በሆይሶድ ዕምነት፣ የሰው ልጅ ከአምላኮች ቁጥጥር ውጭ በማሰብ ኃይሉ የሚያደርገው ምንም ነገር እንደሌለና የራሱንም ኑሮ በአምላኮች ፈቃድ ብቻ ሊያደራጅና ቴክኖሎጂዎችንም ሊፈጥር እንደሚችል ብቻ ይታመን ነበር። ይህ ዕምነት ለብዙ መቶ አመታት በግሪክ በተለያዩ ደሴቶች በሚገኙ ህዝቦች ጭንቅላት ውስጥ በመስፈር አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን ሊወስን ችሏል።

       ከክርስቶስ ልደት በፊት ከስድስት መቶ ዓ.ም ጀምሮ ግን ሁኔታው እየተለወጠ ይመጣል። በተለይም በሩቅ ንግድ አማካይነት ከሌላው ዓለም ጋር ግኑኝነት ያላቸው ደሴቶች ወደ ውስጥ በንግድም ሆነ በዕደ-ጥበብ ሙያ እየዳበሩና ህዝቦችም ራሳቻውን መጠየቅ ይጀምራሉ። ስለዚህም ቀድሞ በሆሜር የተደረሰውንም ሆነ በዐይናቸው የሚያዩትን የተፈጥሮ ባህርይ መለዋወጥ ዝም ብለው መቀበልና ማመን እንደሌለባቸው ይረዳሉ። የተፈጥሮ አደጋዎች ካለምክንያት ሊከሰቱ እንደማይችሉ ራሳቸውን በመጠየቅ፣ አንድ ተፈጥሮአዊ አደጋ ካለምክንያት ሊከሰትና በአምላኮች ቁጣ በሰዎች ላይ ሊመጣ የሚችል አደጋ እንደሌለ ይገነዘባሉ ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ክፍለ-ዘመን  የነበሩ ሰዎች  የመንፈስንና የአእምሮን ሚና የተገነዘቡ አልነበሩም። በማሰብ ኃይላቸውም የተፈጥሮንና የራሳቸውን ሁኔታ ሊለውጡ የሚችሉ አይመስላቸውም ነበር። በስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት አዳዲስ ምሁራን ግን ማንኛውም ነገር በአእምሮ ውስጥ ሊታሰብ እንደሚችልና፣ ወደ ውጭ የሚከሰቱትንም ነገሮች ውስጣዊ ህግ መረዳት እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። ከሶክራተስ በፊት የነበሩት ተመራማሪዎች በህዋ ውስጥ የሚከሰቱትን ነገሮች ሁሉ መመርመርና መረዳት እንደሚችሉ ይደርሱበታል። የመጀመሪያውም አባባለቸው፣ ማንኛውም ነገር ካለ ምክንያት ሊከሰት አይችልም የሚል ነው። ስለዚህም፣ ህዋ የራሱ ተፈጥሮአዊ ህግ እንዳለውና በውስጥ ባሉት የተፈጥሮ ህግ መሰረት ወደ ውጭ ሊታዩ የሚችሉ ነገሮች እንደሚከሰቱ ያመለክታሉ። ስለዚህም ሆዳችንን ሲያመን እንደሚጎረብጠንና አንዳንድ ጊዜም በመንጓጓት ጩኸት እንደሚሰማ ሁሉ፣ በህዋ ውስጥ በሚገኘው ውስጣዊ ህግ መሰረት ነጎድጓድም ሆነ መብረቅ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። በ500 ዓ.ም ከክርሰቶስ ልደት በፊት ይኖር የነበረው ሄራክሊት የሚባለው ፈላስፋ ካለምንም ምክንያት ሊከሰት የሚችል ነገር ተብሎ ይታመንበት የነበረው የተፈጥሮ አደጋ ወይም መብረቅ መመርመር እንዳለበት በማመልከት፣ ህዋን የፈጠሩ በእዚያ ጊዜ ይመለክባቸው የነበሩ አምላኮች ሳይሆኑ፤ ህዋ የነበረና፣ ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር ዘለዓለማዊ ነገር ነው ብሎ የሆሜርንና የሆይሶድን ዕምነት ውድቅ ያደርጋል። ስለሆነም፣ የመንፈስንና(Soul) ስነ-አእምሮአዊ (Psychology)መኖርና ትርጉም በማሳየት፣ የሰው ልጅ አካልና መንፈስ እንዳለው ያረጋግጣል። ሄራክሊትም፣ መንፈስ ገደብ-የሌለውና ጥልቀቱ በፍጹም ሊደረስበት እንደማይችል ይረዳል። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን ካንቀሳቀሰ ብዙ ነገሮች ሊታዩት እንደሚችልና፣ የተለያዩ ነገሮችንም እንደሚፈጥር ነው።

               ይሁንና በጊዜው ብቅ ያሉት ከሶክራተስ በፊት የነበሩት ፈላስፎች ለህዋና ለነገር መፈጠር በሆነው ምክንያት ላይ ስምምነት አልነበራቸውም። ታለስ የሚባለው የመጀመሪያው ፈላስፋ ሁሉም ነገር ከውሃ አንደፈለቀ አበሰረ። በታለስ ዕምነት ውሃ ኃይለኛና በጣም አስፈላጊ ስለሆነ የነገሮች ሁሉ ምንጭ ነው አለ። ውሃ በጣም ሲቀዘቅዝ ወደ በረዶነት ይለወጣል። በጣም ሲፈላ ደግሞ በመተነን ወደ አየር ውስጥ ይገባል። ስለዚህም በታለስ ዕምነት ውሃ የሁሉም ነገር መነሻ ነው። በሌላው የቅድመ-ሶክራተስ ፈላስፋ አናክሲማንድር ተብሎ በሚታወቀው ግን ውሃ በሙቀትም ሆነ በቅዝቃዜ ጊዜ ስለሚለወጥ የተፈጥሮ ወይም የነገሮች ሁሉ መነሻ ሊሆን አይችልም አለ። በአናክሲማንድር ዕምነት የሁሉም ነገር መነሻ ተለዋዋጭ ያልሆነ፣ መነሻና ማለቂያ የሌለው ዘለዓለማዊ ነገር መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት ውሃ፣ አየርና እሳት ለሌሎች ነገሮች መነሻ ወይም ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም አለ። በአናክሲማንድርም ዕምነት ተነጣጥለው በሚገኙ ነገሮች መሀከል መለዋወጥና አንድኛው ሌላውን ሰለሚያጠፋው፣ ለምሳሌ ውሃ እሳትን፣ ውሃና ወይም እሳትን እንደነገሮች ሁሉ መነሻ አድርገን ከወሰድን በተፈጥሮ ውስጥ መዘበራረቆችና መደበላለቅ ይበዛል። በዚህም ምክንያት የሌሎች ነገሮች ሁሉ መነሻ ተለዋዋጭ ያልሆነ ነገር መሆን አለበት በማለት ተናገረ። አናክሲሜነስ በሚባለው ፈላስፋ ዕምነት ደግሞ የነገሮች ሁሉ መነሻ አየር ነው። ምክንያቱም አየር ሁሉም ቦታ ስለሚኖርና በጣም የረቀቀ ስለሆነ የነገሮች ሁሉ መነሻ መሆን  አለበት።  ሄራክሊት የተባለው ፈላስፋ ደግሞ ልክ እንደ አናክሲማንድር በሁለት ነገሮች ላይ መገረም ጀመረ። አንደኛ፣ በነገሮች መለዋወጥና የማያቋርጥ እንቅስቃሴ፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ በነገሮች መሀከል ቅራኔ መኖርና የማያቋርጥ ትግል በመገረም አንድ እነዚህን ሁሉ የሚገዛና የሚያንቀሳቅስ ኃይል መኖር አለበት ብሎ አመነ። ሰለሆነም በሄራክሊተሰ ዕምነት፣ ዓለም በጠቅላላው ወደ ማሰብ ኃይል በመለወጥ ተቃርነው የሚገኙ ነገሮች እንደገና ወደ ስምምነት የሚያመሩ መሆን አለባቸው አለ። ሁለተኛ፣ ሁላችንም ሟች እንደመሆናችን መጠን ዕውነተኛውን ነጻነት የምናገኘው ከሞት በኋላ ነው። ሶስተኛ፣ በምድር ላይ ዕውነተኛ ነጻነትን የመቀዳጀቱ ጉዳይ ለጥቂት ለተመረጡና የመንፈስ ኃይላቸው ከፍተኛውን ቦታ ለያዙ ሰዎች የተሰጠ ሲሆን፣ በመንፈስ ኃይል እየተመሩ የእግዚአብሄርን ዓላማ ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው። በሄክራሊትስም ፍለጋ፣ በህዋ ላይ የሚታዩ  ነገሮችን መመርመርና ውስጣዊ ህጋቸውን መረዳት አስፈላጊ ሲሆን፣ በዚህች ዓለም  ላይ የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ(Logos) ሚናውን እንዲረዳ ማድረግ ነው። በመሆኑም በመጀመሪያ፣ ኮስሞስን ወይም ሰርዓት ያለውን ዓለም በጭንቅላት ውስጥ መቅረጽ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ዓለም አቀፋዊ ወይም ሃሳባዊ መሰረቱን መረዳት ያስፈልጋል። በሶስተኛ ደረጃ፣ ዕውነተኛውን የሎጎስን ትርጉም መረዳትና በግልጽ ወደ ውጭ ማውጣት ያስፈልጋል።  ምክንያቱም የሰው ልጅ ማንነቱን መገንዘብ የሚችለውና፣ ቋንቋንና ልዩ ልዩ ነገሮችን ሊፈጥር የሚችለው በሎጎስ አማካይነት ስለሆነ ብቻ ነው። በሄራክሊተስ ዕምነት ተፈጥሮም ሆነ የሰው ለጅ ኑሮ በቅራኔዎች ህግጋት የሚተዳደር ነው። ብርሃንና ጨለማ፣ ርሃብና ጥጋብ፣ ሰላምና ጦርነት … ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የሰውን ልጅ የሚከተሉትና በጭንቅላቱ ውስጥ የሚላወሱ ስለሆነ፣ በማሰብ ኃይል ይህንን የቅራኔ ህግጋት እንዴት መቋቋምና መፍታት ይቻላል ነው። በሄራክሊትስ ዕምነት የሰው ልጅ ይህንን ሲገነዘብና ለመፍታት ሲሞክር ለዕውነተኛ ነጻነት የሚሆነውን መሰረት ይጥላል። እዚህ ላይ ተፈጠሮአዊ የሆኑ የቅራኔ ህግጋትንና ሰው ሰልሽ የሆኑ ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎችን፣ ለምሳሌ ጦርነት ወይም ረሃብ መሀከል ለውን ልዩነት መረዳት ያሰፈልጋል። የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ ጦርነትንም ሆነ ረሃብን ማስወገድ ቢችልም ጨለማን ግን ሙሉ በሙሉ ወደ ብርሃንነት ሊውጥ አይችልም። ፓርሜናይድስ የተባለው ተመራማሪ ደግሞ፣ የተፈጥሮ ልዩ ልዩ ነገሮችንና ገጽታዎችን በመመርመር እነዚህን ነገሮች ወደ ተራ ጣምራዊ ነገሮች መለወጥ እንደሚቻል አመለከተ። ለምሳሌ ብርሃንና ጨለማ፣ መኖርና አለመኖር በአንዳች ኃይል ወይም ነገር የተፈጠሩ ሲሆን በተለያየ መልክ በተለያዩ ነገሮች ላይ ይታያሉ አለ። ስለዚህም እነዚህ ተቃርነው የሚገኙ ነገሮች ከሰውነትም ጋር የተዋሃዱ ስለሆኑ የሰው ልጅም በግልጽ የሚያያቸውን ነገሮች እንደዚያው እንዲመለከታቸው ተገዷል ይላል። ከፓርሜናይድስ በፊት የነበሩ ፈላስፎችና ራሱም ጭምር ይህ ዕምነት እንደነበራቸው ሲገልጽ፣ ይህ መኖርንና አለመኖርን አደባልቆ ማየት ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ሊፈታ የማይቻል ቅራኔ ውስጥ ይከተናል አለ። ስለዚህም በፓርሜናይድስ ዕምነት ዕውቀት በማሰብ ኃይል የሚገኝ ሰለሆነ ይህም በሚኖር ወይም በተጨባጭ ነገር ላይ የተመረኮዘ ነው። የማይኖርን ነገር(not-being) እንደ ዕውቀት መነሻ አድርገን  ልንወስድ አንችልም። በፓርሜናይድስ ዕምነት የሚታዩ ነገሮችን ባህርይ በአእምሮ አማካይነት ሎጂካዊ በሆነ ነገር መመርምር  እንደሚቻል ሲያሳይ፣ ዕውቀት ከአዕምሮ ውስጥ ሳይሆን በተጨባጭ ነገሮች ላይ መመርኮዙንና በምርምርም ሊደረስበት እንደሚችል አመነ። ስለሆነም ይህ የፓርሜናይድስ ጥያቄና ምርምር እነሄራክሊትን ፈተና ውስጥ ከተታቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብቅ ያሉትና የተለያየ ፈለግ ይከተሉ የነበሩት ተመራማሪዎች በአንዱ ምርምር ባለመርካት በተከታታይ አዳዲስ ጥያቄዎችን ማቅረብ ጀመሩ። ባጭሩ ይህ የሚያመለክተው ምንድነው?  በአንድ የታሪክ ወቅት ብቅ ያለ የምርምር ዘዴ ያኔውኑ ተቀባይነት አግኝቶ በዚያው መቀጠል እንዳልተቻለ ነው። በእየአንዳንዱ የታሪክ ወቅት የሚነሳ የምሁር ትውልድ ሙያዬ ብሎ የያዘው በቀድሞዎቹ ሳይረካና እንደገና በመጠየቅ የሚያረካ መልስ ለማግኘት መጣር ነበር። አንዱ ያነሳው ወይም የወረወረው ሃሳብ ዝም ብሎ በጭፍን መቀበል እንደማይቻል ያስመሰከረ የምርምር ዘዴ ነው። ከሶክራተስ በፊት የነበሩት ፈላስፋዎች፣ በአጠቃላይ ሲታይ፣ ነገር(Matter) ለሚባለው የተለያየ ባህርይና ምክንያት በመስጠት በጭፍን ዕምነት ላይ የተመረኮዘውን አመለካከት ውድቅ በማድረግ የመጀመሪያውን በአእምሮ ሊደረስበት የሚችለውን የምርምር መሰረት ጣሉ። ለሶክራተስ፣ ለፕላቶና ለአርስቲቶተለስ የመጀመሪያውን የፍልስፍና መንገድና የምርምር መንገድ ቀየሱ። ከሶክራተስ በፊት የነበሩት ፈላስፋዎች በህዋ ውስጥ ያሉ ነገሮች የተሳሰሩና፣ ምክንያቶቻቸውና ክስተቶቻቸውም በዚያው በህዋ ውስጣዊ ህግ መሰረት ሊደነገጉ እንደሚችሉ አረጋገጡ።

       ይህ ብቻ አይደለም፤ ከሶክራተስ በፊት ለነበሩት ፈላስፋዎች የጭንቅላት ምርምር ምክንያት በጊዜው የሰፈነው የጥቂት አሪስቶክራቶች መሳከርና መባለግ፣ እንዲሁም በህዝቡ ላይ የሚያደርሱት ጭቆናና የእርስ በርስ የወንድማማቾች መጨፋጨፍ ነበር። ከቁጥጥርም ሲወጡ ህዝቡን ለርስ በርስ ጦርነት በመጋበዝ እንደሚያጫርሱት በመመልከት፣ ይህ የማያስፈልግ ድርጊት በአምላኮች ሳይሆን በሰዎች፣ በተለይም በገዢው መደቦች እንደሚፈጠሩ ነው። የሰዎች የማሰብ ኃይል የጠበበ ከሆነ ድርጊታቸው ሁሉ ወደ መጥፎ ነገር እንሚያመራ በመመልከት፣ ህዋ ራሱ የተወሰነ ስርዓት እንዳለውና በውስጣዊ ህግም እንደሚንቀሳቀስ በማመልከት፣ የሰው ልጅም በአስተሳሰቡ ውስጥ ስርዓትንና ስምምነትን(Harmony and Order) በማዳበር ወደ ቀና ተግባር ማምራት እንዳለበት ማስተማርና መስበክ ጀመሩ።  ስለሆነም በግሪክ ዓለም ውስጥ አርቆ-አሳቢነት(Rationalism) ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ መሟላትን፣ መጠቃለልን፣ አንድ የሚያምር ቅርጽ ያለውንና በስርዓት የተደራጀን ሁኔታን የሚያመለክት ነው። ይህን የማያሟላ ከሆነ ደግሞ ዝብርቅርቅነትና ውዥንብር የበዛበት፣ ሁሉም በየፊናው  በራሱ ዓለም ውስጥ የሚሸከረከርበትና  ወደ ህብረተሰብአዊ ቀውስ በማምራት  የሰውን ልጅ የመኖር ትርጉም በማሳጣት ዘለዓለሙን እንደተንቀዠቀዠ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። በፕላቶ አባባል፣  የሰው ልጅ ዋናው ችግር የማሰብ ኃይል ያለመዳበር ጉዳይ ነው። ሁሉንም ነገር በጠባቡ የመመልከት ችግር ነው። አርቆ-ማሰብ ሳይቻልና በዚህች ዓለም ላይ ሲኖር ምን ማድረግ እንዳለበት መገንዘብ ሳይችል ሲቀር፣ ድርጊቱ ሁሉ በሚሆን በማይሆን ላይ በማትኮር ህብረተሰብአዊ ትርምስን ይፈጥራል። ለራሴ ብቻ ብሎ ሲያስብና ስግብግብነትን ሲያስቀድም ለሌላው ምሳሌ በመሆን አንድ ህዝብ ርስ በርሱ እንዲበላላ መንገዱን ይከፍታል። ከ20 ዓመት ጀምሮ በአገራችን የተፈጠረውና መረን የለቀቀው አገዛዝ ከላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ ነው የሚያረጋግጥልን።

       ይሁንና ከሶክራተስ በፊትም ሆነ በኋላ የተፈጠረው አስተሳሰብ ካለምክንያት  አይደለም። በስድሰተኛው ክፍለ-ዘመን አዮን በሚባለው ደሴት የዳበረው የንግድና የዕድ-ጥበብ ዕድገት፣ እንዲሁም ደግሞ ከውጭ በሩቅ ንግድ አማካይነት የገባው አስተሳሰብና ባህል ወደ ውስጥ፣ ባህላዊ ለውጥ እንዲፈጠር መንገዱን ይከፍታል። አዲስ ባህል ሲፈጠርና ቀስ በቀስም ሲስፋፋ አንዳንድ የታያቸው ምሁራን ራሳቸውንና ሚናቸውን መጠየቅ ይጀምራሉ። የሰው ልጅ በዘልማድ ከትውልድ ወደ ትውልድ በተላለፈ የአኗኗር ስልት እንዳማይኖር በመረዳት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተንሰራፍቶ የነበረውን ጦርነትን ጋባዥና የማደንቆሪያ ቅስቀሳ ለመቋቋም ታጥቀው ይነሳሉ። አነሳሳቸውና የጥያቄ አቀራረባቸው ግን ጦርነት እንጀምር አልነበረም። አነሳሳቸው የማሰብን ኃይል ማደባርና የመንፈስን ኃይልና ገደበ-አልባነት በመገንዘብ ለሳይንስ በር መክፈት ነበር። የሰው ልጅ ራሱን ነጻ ሊያወጣ የሚችለው ራሱን ደጋግሞ በመጠየቅና በመመራመር ብቻ እንደሆነ ይበልጥ ይረዳሉ። የሰው ልጅም፣ በራሱ አምሳል በሆነውና የተፈጥሮ ተገዢና ሰለባ ሊሆን የሚችለው ራሱን መጠየቅ ያልቻለ እንደሆነ ብቻ መሆኑን ይገነዘባሉ።

       ሆኖም ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ፈር እንዲይዝ ከተፈለገም ደግሞ ከላይ የጥገና ለውጥ መደረግ ነበረበት። መረን የለቀቀ አገዛዝ መፈናፈኛ በማይሰጥበት ቦታና የኑሮ ትርጉም ወደ ጦርነት በተለወጠበት ሁኔታ ውስጥ የግዴታ የገዢ መደቦችን አስተሳሰብ መለወጥ ያስፈልጋል። አንዳንድ የአስተሳሰብ ለውጥና የእኩልነት አስፈላጊነት ጭላንጭሎች በሆሜር፣ በተለይም በሆይሶድ ዘመን ይታዩ እንደነበር ግልጽ ነው። በተለይም እሮሮዎችና መረንን የለቀቀ የጭቆና አገዛዝን የመቃወም መንፈስ ይሰማ የነበረው በተራው ህዝብ ዘንድ መሀከል ሳይሆን ከውስጥ የገዢው መደብ በነበሩ አባሎች ነበር። እንደዚህ ዐይነቱ በገዢው መደብ ውስጥ የነበረው የአስተሳሰብ ለውጥና ውስጣዊ ቅራኔ ግን  የአሪስቶክራሲው መደብ አባል በነበረውና በፍልስፍናና በድራማ ራሱን ባነጸው ሶሎን በሚባለው መሪ የግዴታ ስልጣን በመያዝ ሪፎርም መደረግ እንዳለበት ታመነበት። ስልጣን ከያዘ በኋላም የወሰዳቸው ርምጃዎች በገበሬው ላይ የተጫነውን ዕዳ በሙሉ ማሰረዝ ነበር። በተለይም ዜጎች ተብለው ለሚጠሩት ሁሉ ሙሉ ነጻነት እንዲያገኙ በማድረግ የሃሳብ መንሸራሸር እንዲዳብርና በቲያትርና በትራጄዲ መልክ የገዢው መደቦች አስተሳሰብም ክፍት እንዲሆን በማድረግ የባህል ለውጥ እንዲደረግ መንገዱን ከፈተ። እሱ በቀደደው ፈለግ እንደገና አዳዲስ ተመራማሪዎች በመፍለቅ ለግሪክ ስልጣኔ ልዩ ዕምርታን ሰጡት። ሶክራተስና ፕላቶን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ የማቲማቲክ፣ የአርኪቴክቸር፣የድራማና የግጥም እንዲሁም የልዩ ልዩ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደ አሸን ሊፈልቁና የድሮውን አስተሳሰብ ሊጋፈጡት የቻሉት በሶሎን ጥበባዊ ስልት ነው። ኸርቢግና ስኔል በሚባሉት ታላላቅ የጀርመን ተመራማሪዎችና በፕሮፌስር ዶድስ የተደረሰበትም ምርምር የግሪክ ስልጣኔ ከአምልኮአዊነት ወደ ሳይንሳዊ ምርምርና ወደ አጠቃላይ ስልጣኔ ሊያመራና ሊዳብር የቻለው በባህል ለውጥ አማካይነትም የአስተሳሰብ ለውጥ በመምጣቱ ብቻ ነው። ለአንድ ህብረተሰብ ለውጥና ስልጣኔ የግዴታ ባህላዊ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ሶስቱም ተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አያሌ ጥናቶች ያመለክታሉ። ስለሆነም፣ ማንኛውም ህብረተሰብ ዕውነትን ለመፈለግና የስልጣኔን በር ለመክፈት የሚችለው ከውስጥ ለመንፈስ ተሀድሶው የሚረዳው የባህል ለውጥ ሲያደርግ ብቻ ነው። የባህል ለውጥ ማለት ደግሞ ዛሬ በአገራችን እንደሚታየው ቅጥ ያጣ መባለግና፣ የተበላሸ የዘፈንና የድራማ አሰራር ሳይሆን፣ የበለጠ አርቅቆ ማሰብን የሚረዳና መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ወደ ውስጥ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብአዊ ግንባታ የሚያመቻች መሆን አለበት። በተጨማሪም የባህል ለውጥ ማለት እያንዳንዱ ግለሰብ ነጻነት እንዳለው ሲሰማውና በመፍጠር ኃይሉ የራሱን ኑሮ ለውጦ ከሌላው ተመሳሳይ ዜጋ ጋር ህብረተሰብአዊ ለውጥ ማምጣት የቻለ እንደሆን ብቻ ነው። የባህል ለውጥ ማለት በአንድ አገር የሚኖርን ሀዝብ የሚያስተሳስር፣ በክልል ከልሎ የማያናቁር፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሰው መሆኑን ተገንዝቦ ከሌላው ጋር በመጋባትና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ማንኛውም ሰው በእግዚአብሄር አምላክ የተፈጠረና አንደኛው በሌላው ላይ የሚነሳና የሚያጠቃው ሳይሆን፣ ሰው ለሰው መድሃኒቱ ነው የሚለውን በጭንቅላቱ ውስጥ ቋጥሮ ለቁም ነገር ሲነሳ ብቻ ነው።

       ይህም ማለት ማንኛውም ዜጋ ውስጣዊ የመንፈስ ነጻነት ማግኘት አለበት። ራሱን ማወቅ አለበት። ከላይ እንዳየነው ከሆሜር በፊትና በሆሜር ዘመን የነበሩ ህዝቦች ይህ ዐይነቱ ውስጣዊ የመንፈስ ነጻነት አልነበራቸውም። ዕምነታቸው ሁሉ በአምላኮች ላይ የተመረኮዘና ህይወታቸው ሁሉ በእነሱ ይደነገጋል ብለው ይገምቱ ስለነበር ውስጣዊ የመንፈስ ነጻነት አይሰማቸውም ነበር። በጭንቀትና በፍርሃት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ነበሩ። እኔ ነኝ የራሴ ህይወት ደንጋጊ ብለው ማሰብ ሲጀምሩና ስሜትና ፍላጎት እንዳለቸው ሲረዱ በትከሻቸው ላይ የተጫነውን ከባድ ጭነት አሽቀንጥረው መጣል እንዳለባቸው ተረዱ። ይህ ውስጣዊ የነጻነት ስሜት ከመሰማቱና ለራስ ብሎ ከማሰብ በፊት ከቶውንም በአገዛዞች የተጫነውን የውሸት ሸክም መጣል እንደማይቻል ግልጽ ነበር። ስለዚህም የግሪክ ህዝቦች፣ በተለይም ፈላስፎች ዋናው የሰው ልጅ ጠላት ይህንን ውስጣዊ ነጻነት ያለማወቅና በራስ ህይወት ላይ መደንገግን ለመረዳት ያለመቻል ግልጽ መሆን ጀመረ። ወደ አገራችንም ስንመጣ ዋናው ችግር ይህንን ውስጣዊ ነጻነት በማሰብ ኃይል ለመቀዳጀት ያለመቻል ነው። ከገዢውም መደብ ውስጥም ሆነ ከህዝቡ ዘንድ ሊፈልቅ የሚችል የአስተሳሰብ ነጻነት ብቅ ለማለት ባለመቻሉና፣ በተለይም በስነ-ጽሁፍ መልክ የሁኔታውን አስከፊነት ሊገልጽ የሚችል ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሰፊው ብቅ ሊል ባለመቻሉ ህዝባችን በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። ዛሬ ሰላይ በአገሪቱ ምድር ተሰማርቶ ህዝባችንን እንደሚሰልለውና በጭንቀት ዓለም ውስጥ እንደሚኖር ሁሉ፣ ግሪኮችም አምላኮች ይከታተሏቸው ይመስል በፍርሃት የተዋጡ ነበሩ። ይሁንና በግሪክ  ከስምንቶ መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው አስተሳሰብ የሰዎች ዕምነት ነበር። ተጨባጭ አልነበረም። የዛሬው የአገራችን ሁኔታና የስለላ መረብ ግን ተጨባጭ ነው። የሚታይና በእርግጥም በተግባር የሚያስፈራም ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ሁለቱንም የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። የዛሬው የወያኔው አገዛዝ በተበላሸ ርዕዩ የሰማንያ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል እኔው ብቻ ነኝ ልወስን የምችለው ብሎ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር አገራችንን ወደ ማይሆን አቅጣጫ እያመራ ነው። አቶ መለሰ ትንሹ በተንኮል የተሞላው 㗹የግሪክ አምላክ ዞይስን የሚመስሉ ናቸው። ከስሮቻቸው ያሉት ደግሞ ትንንሾቹ መጥፎን ነገር ፈጣሪ አምላኮች ናቸው ማለት ነው። ይሁንና ግን በአገራችንም እንደግሪኮቹ የሰፈነው አስቀያሚ ስርዓት በሰዎች እንጂ በአምላኮች አይደለም። ስለዚህም ልክ እንደ ስድስተኛው ምዕተ-ዓመት የግሪኮች ስልጣኔ አጀማመር የኢትዮጵያም ህዝቦች እንደዚያን ጊዜው ጥቂቶቸ በፈጠሩት የብልግና ስርዓት መታሸትና ዘለዓለማዊ ፍዳቸውን ማየት እንደሌላባቸው መረዳት አለባቸው። የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የማሰብ ኃይል ብቻ መወሰን እንደሚችሉ መገንዘብ አለባቸው። በውሸት ዓለም ውስጥ መኖር የለባቸውም። የገዢዎችንና የበላዮቻቸውን የድንቁርና አገዛዝ የአምላኮች ተልዕኮ ነው ብለው አሜን ብለው በመቀበል ፍዳያቸውን ማየት የለባቸውም። ስለዚህም፣ በዚህ ዐይነት አስቀያሚ ኑሮ እስከ መቼ ድረስ መግፋት ይቻላል?   ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው።

       ወደ ፕላቶ ስንመጣም ያዳበረው የአርቆ-አስተሳሰብ አመለካከት በተወሰነ የባህልና አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ ዘመን ውስጥ እንደነበረና የዚያም ውጤት መሆኑን መገመት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ እየተፋፋመና እየዳበረ የመጣው ምሁራዊ እንቀስቃሴ የበለጠ የአመለካከቱን አድማስ ሊያሰፋው ችሏል። በተጨማሪም  ለራስ ጥቅም ብቻ መቆምና ኃያልነትንና ገናናነትን ለመሻት መሯሯጥ አንድን አገር ወይም ስልጣኔ እንደሚያፈርሰው ይመለከታል። በአርቆ-አስተዋይነት ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ ፍርድ እስከሌለ ድረስ የፍርደ-ገምድሎች አገዛዝ ህብረተሰቡን ችግር ውስጥ እንደሚከተው ያወጣል፣ ያወርዳል። ሰለሆነም የተከታዩ ትውልድ ዕድል እንደሚበላሽ ይገነዘባል። በተጨማሪም በአስተማሪው በሶክራተስ ላይ የደረሰበት ውንጀላና የሞት ፍርድ በአርቆ-አስተዋይነቱና በሞራል ፍልስፍናው እንዲገፋበት ይጠነክራል። የሰዎች ባህርይ ተለዋዋጭ መሆኑን ከማንኛውም ምሁር በይበልጥ በመገንዘብ የሞራልንና የስነ-ምግባርን እንዲሁም ደግሞ ጥሩ ስራን መስራት አስፈላጊና፣ በዚህ ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር መደረግ እንዳለበት ለተማሪዎቹ ያስረዳል። እነዚህ ሁኔታዎች ፕላቶንን የበለጠ በአርቆ-አስተዋይነትና አሳቢነት ምርምሩ እንዲገፋበት በማድረግ አንድን ነገር ለመረዳት ከሚታዩ ነገሮች ዘልቆ መሄድ እንደሚያስፈልግ ያምንበታል። ምናልባትም ከሶክራተስ ቀጥሎ የሰውን ልጅ የህሊና አወቃቀር በጥልቀት የተረዳና ያስፋፋ ቢኖር እንደ ፕላቶ የለም ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ የፈለቁት የተለያዩ የፍልስፍና ዘርፎች፣ በተለይም የጀርመኑ ፍልስፍና በፕላቶናዊ የፍልስፍና ምርምር ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከታላቁ የሃይማኖት፣ የፍልስፍናና የዕውቀት ተመራማሪና የመጀመሪያው የካልኩለስ መሰረት ጣይ ከቄስ ኩዛኑስ ጀምሮ፣ ኮፐርኒስ፣ ኬፕለርና ላይብኒዝ፣ እነዚህ ሁሉ የሳይንስ ተመራማሪዎች ሊሆኑ የበቁት የፕላቶንና የሶክራተስን የምርምርና ጭንቅላትን የማስጨነቅ ዘዴ በመመርኮዝ ነው። የግሪኩንም ስልጣኔ ሆነ የኋላ ኋላ ወደ አውሮፓ የተሸጋገረውን ስንመለከት በግሪክም ሆነ በአውሮፓ ምድር የፈለቁት ፈላስፋዎች በራሳቸው ክልል የሚሽከረከሩ ሳይሆኑ ሃሳብ ለሃሳብ የሚለዋወጡና እንዲያም ሲል በተለያዩ አስተሳሰቦችም ላይ የሚከራከሩ ነበሩ። በተጨማሪም ደቀ-መዝሙርን ማፍራትና ዕውቀት ተከታታይነት እንዲኖረው ማድረግ በግሪክም ሆነ በአውሮፓ ምድር እንደ ባህል የተወሰደ ነበር። በዚህ ዐይነት ውስጣዊ ግኑኝነትና ኃይል እንዲሁም የሃሳብ ተከታታይነት፣ ሃሳብንም ተግባራዊ በማድረግ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ የግሪኮችም ሆነ የአውሮፓውያን ባህል ሊሆን በቅቷል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህም የሚያመለክተው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በሃሳብ የሚገናኙ ምሁራን እስካልተፈጠሩ ድረስና፣ አንደኛው ሌላውን በማዳመጥ የሃሳብ ልውውጥና ክርክር እስካላደረጉ ድረስ ለዕድገት የሚደረገው ጉዞ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። በብዙ የአፍሪቃ አገሮች፣ በተለይም በአገራችን ምሁር ዘንድ የሚጎለው በሃሳብ ዙሪያ ክርክር ለማድረግ አለመቻልና ሁሉም በየፊናው የራሱ የግል ፍልስፍና ያለው ይመስል ብቻውን መክነፉ ነው። በአውሮፓ ምድር ፍልስፍናን ማስፋፋት የተጀመረው በ13ኛው ክፍለ-ዘመን ገደማ ሲሆን፣ ቶሎ ብሎ ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው ግለሰቦች ጋር ግኑኝነት መፍጠርና ሃሳቡም በአንድ አካባቢ ብቻ ታፍኖ እንዳይቀር ትግል ማድረግ ነበር። ይሁንና የግሪኩ አስታሰሰብ በምዕራብ አውሮፓ ምድር በአሸናፊነት ለመውጣትና ሳይንስና ቴክኖሎጂ የህዝቡን ኑሮ ወሳኝ ለመሆን የበቁት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው። ጠጋ ብለን እንመልከት።

ዕውነት ሲያሸነፍ- የሳይንስ የበላይነት ሲረጋገጥ !

         የአውሮፓ ሬናሳንስ የግሪኩ ስልጣኔ በአዲስ መልክ የታደሰበት(Re-play) ነው ማለት ይቻላል። እስከ ዘመነ-ሬናሳንስ ድረስ የአውሮፓ ህዝብ በውዥንብርና በጨለማ ዓለም ውስጥ ይኖር ነበር። ይሁንና ግን ምንም ዐይነት ፈጠራ አይካሄድም፤ ከተማዎችም አይገነቡም ማለት አይደለም። በስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከ አስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ፊዩዳሊዝምና የካቶሊክ ሃይማኖት የብዙ ምዕራብ አውሮፓ ህዝቦችን አስተሳሰብና የኑሮ ፍልስፍና ይቆጣጠሩ ነበር።

       ስለሆነም የግሪኩ ስልጣኔ ቀስ ቀስ እያለ ሰርጎ ሲገባ አንድ ወጥ አስተሳሰብ ብቻ ለማዳበር በፍጹም አልተቻለም። ህዝቦችን ለአገር አቀፍ ተግባር ሊያንቀሳቅሳቸውና እንደመመሪያ ሊሆን የሚችል አመለካከት በአሸናፊነት አልወጣም። የፕላቶንን አስታሳሰብ በሚከተሉና የአርሰቲቶሊስንና እንዲሁም ደግሞ የፕላቶንን ፍልስፍና በሌላ መልክ በሚተረጉሙ መሀከል የሃሳብ ልዩነቶች በግልጽ ይታዩ ነበር። በይማኖት አካባቢም እንደዚሁ ውዝግብ በመፈጠር ዓለማዊና ዘለዓለማዊውን ዓለም/የእግዚአብሄሩን ዓለም/በሚከተሉ መሀከል የሃሳብ ግጭቶች በጉልህ ይታዩ ነበር። አንዱ ሌላውን በመቃወም እርስ በርስ የሚዋጉበትና፣ አንደኛው አስተሳሰብ በአሸናፊነት ሊወጣ ያልቻለበት ሀኔታ በግልጽ ይታይ ነበር። ስለዚህም ወደ ሬናሳንስና ሃይማኖትን ማሻሽል ወይም በሱ-ውስጥ የጥገና ለውጥ(Reformation) አድርጎ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ለማምጣት የአውሮፓ ህዝብ አስቸጋሪ ጉዞ መጓዝ ነበረበት። በአስራአምስተኛው ክፈለ-ዘመን የሃይማኖትንና የአርስቲቶለስን አስተሳሰብ እየተቃረነ የወጣው በማጂክ ላይ የተመሰረተ አመለካከት የእግዚአብሄርን ምስጢር በምርምር ማግኘትና ከሱም ጋር መረዳዳት እንደሚቻል ያበስራል። በአዲሱ የማጂክ አስተሳሰብ ዕውቀት በደመ-ነፍስና(Intuition)፣ እየመላለሱ በመጠየቅና የተፈጥሮን ህግ ለመረዳት በሚደረግ ጥረት ሊደረስበት እንደሚችል ያመልክታል። ስለሆነም ህይወትና ተፈጥሮ ክንውናዊና ውስጠ-ኃይል ያላቸው እንጂ ቋሚ እንዳልሆኑ ያመልክታል። ይህ አዲሱ አመለካከት ለኮፐርኒከስም ሆነ ለተከታዩ ትውልድ የቀድሞውን በተፈጥሮ ላይ የነበረውን አመለካከት እንዲከልሱት በሩን ይከፍትላቸዋል። በአዲሱ የምርምር ዘዴ በመረዳት፣ ኮፐርኒከስ የአርስቲቶለስንም ሆነ የካቶሊክ ሃይማኖትን በመሬትና በፀሀይ ላይ የነበራቸውን አቋም ውድቅ ያደርጋል። ኮፐርኒከስ መሬትና ሌሎች ፕላኔቶች በፀሀይ ዙሪያ እንደሚሽከረከሩ ያረጋግጣል። በተጨማሪም እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ መጥፎ ነው፤ በእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ ነው ጥሩ ነገር ሊሰራና ሊያስብ የሚችለው፤ የሚለውን የካቶሊክ የከረረ አመለካከት አሸቀንጥሮ በመጣል የፕላቶን አስተሳሰብ በአሸናፊነት ይወጣል። በአዲሱ አስተሳሰብ መሰረት፣ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ መጥፎ ሳይሆን በሁኔታዎች ሊሳሳት እንደሚችልና፣ በማሰብ ኃይሉ የተፈጥሮን ምስጢር ሊረዳና ከእግዚአብሄርም ጋር በስምምነት ሊኖር እንደሚችል ይደረስበታል። የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ መንፈሳዊ ባህርይ እንዳለው፣ በዚህ መንፈሳዊ ባህርዩ ብቻ የተፈጥሮን ህግ በመረዳትና በልምድ አማካይነት አዲስ ህይወት ሊመሰርትና ይህም የእግዚአብሄርን ዕምነት ወይም ምስጢር ሊቃረን እንደማይችል በራሱ ከሃይማኖት አካባቢ በፈለቁ ቀሳውስት ይታመንበታል። ይሁንና ግን እግዚአብሄርን ወይም የእግዚአብሄርን ምስጢር ሙሉ በሙሉ ማወቅ በፍጹም አይቻልም። አንድን የተለያዩ ማዕዘናት ያሉትን ስእል(Polygons) በክብ ውስጥ አድርገን እያጠጋጋን ብንስለው ወደ ክቡ ሊጠጋ ቢችልም(The impossibility of changing the square into a circle)  ወደ ክብነት ግን በፍጹም ሊለወጥ አይችልም። ኩዛኑስ የሚባለው የመጀመሪያው ታላቁ የፍልስፍናና ለካልኩለስ መሰረት የጣለው ቄስ በተለይም የሚያረጋግጠው በሚታወቀው መንገድ የማይታወቀውን(to explore the unknown via the known by applying the method of analogy) ምስጢር ማግኘት እንደሚቻልና በመንፈስ ኃይላችን የዩኒቨርስን ህግ መመርመርና ማወቅ እንደሚቻል ነው። ይሁንና ግን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄርን ምስጢር ልናውቅ አንችልም ይላል። ይህ አዲስ አስታሳሰብና ተፈጥሮን የመቃኘት ኃይል ለካቶሊክ ሃይማኖት ከእንግዲህ ወዲያ ተደላድሎ ሊኖር እንደማይችል አረጋገጠለት።

       ይሁንና የሳይንስ ምርምር ቀስ በቀስ በአሸናፊነት ቢወጣም በካቶሊክ መሪዎች የታወቁ ሳይንቲስቶች ክትትል ይደረግባቸውና በግፍ ይገደሉ ነበር። የኮፐርኒከስን አስተሳሰብ የተቀበለውና እሱ ትክክል መሆኑን ያወጀው ጊዮርዳኖ ብሩኖ የሚባለው ፈላስፋ ከፍተኛ ክትትል ይደረግበታል። ሃሳቡን እንዲጥልና ኮፐርኒከሰን እንዲያወግዝ  ትልቅ ግፊት ይፈጥሩበታል። እምቢ ስላለም ወደ እስር ቤት ይወረወራል። የእስር ቤት ቆይታው ግን ከሃሳቡ ፈቀቅ ሊያደርገው አልቻለም። ይህንን የተገነዘቡ የሃይማኖት መሬዎች በሞት እንዲቀጣ ይፈርዱበታል። የመጨረሻ ቃሉንም እንዲህ በማለት ይሰጣል። “You who sentence me are in greater fear than I who am condemned. I have fought, that is much –victory is in the hands of fate. Be that as it may, this at least future ages will not deny me, be the victor who he may-that I did not fear to die. I yielded to none of my fellows in constancy and preferred a spirited death to a cowardly life.”  ይህንን የመጨረሻውን ንግግር ካደረገ በኋላ ይሰቀላል። በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥን አስከተለ።  ሆኖም ግን በከተማዎች ዕድገት፣ በአዳዲስ አስተሳሰቦች መፍለቅና እነዚህም ወደ ተግባርነት መለወጥና ማረጋገጥ፣ የተለያዩ ለሳይንስ ምርምር የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን መስራት፣ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ሳይንስና ነጻ አስተሳሰብ በአሸናፊነት ሲወጡ፣ በዚያው መጠንም አዳዲስ ተመራማሪዎች ብቅ እያሉ የካቶሊክ ሃይማኖት ዕምነት ተቀባይነቱ እንዲቀንስ ያደርጋሉ። ጋሊሌይ ጋሊሊዮ፣ ኬፕለር፣ ኒውተንና ላይብኒዝ የበለጠ እየተመራመሩና በተለይም ለፊዚክስ መሰረት የሚሆን ቲዎሪ ያዳብራሉ። በመሀከላቸው ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት ትተን፣ ሁሉም ተመራማሪዎችም የሚያረጋግጡት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን ሲጠቀም፣ ሲመለከት፣ ሲመረምርና የተፈጥሮን ህግ ለመረዳት ያልተቋረጠ ትግል ሲያደርግ ብቻ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው። ስለሆነም አንድ ጊዜ መንገዱ ከተቀየሰ ለስልጣኔ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚሆን ከዚህ የተሻለ ሌላ ወርቃማ መንገድ እንደሌለ ግንዛቤ ውስጥ ይገባል። ወደ ሌሎች የፍልስፍና ስራዎችም ስንሄድ፣ በተለይም የሰው ልጅ በምድር ላይ ገነትን ሊመስርት የሚችለው የጥበብን ምስጢር ለመረዳት ጥረት ሲያደርግ ብቻ ነው። ካንት፣ ታላቁ የድራማና የፍልስፍና ሰው ሺለር፣ እንዲሁም ጎተ የሚያረጋግጡትና ስራቸውም የሚመሰክርልን የሰው ልጅ በጾም በጸሎት ብቻ ስልጣኔን ሊቀዳጅ እንደማይችል ነው። ጎተ የግሪክን ስልጣኔ በሰፊው ካጠናና ከተመራመረ በኋላ፣ እንዲሁም ጣሊያን ድረስ ሂዶ በግሪክ ፍልስፍናና ምስል መሰረት ላይ የተገነባውን ስልጣኔ ካየ በኋላ ወደ አገሩ ጀርመን ሲመለስ የደረሰበት ድምዳሜ፣ ግሪኮች ብቻ ናቸው ትክክለኛውን መንገድ የቀየሱ ብሎ ነው የተናገረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቫይማር የሚባለው የጀርመን ሊቃውንት የተሰባሰቡበት የፍልስፍናናና የግጥም እንዲሁም የድራማ ከተማ ነው ለጠቅላላው የጀርመን ስልጣኔና ዕድገት በሩን የከፈተው። ስለሆነም፣ የድሮው አስተሳሰብ ከሁሉም አቅጣጫዎች በመከበብ መውጫና መግቢያ አጣ። የሳይንስ ምርምር፣ የአርክቴክቱር ስራዎችና ስዕሎች፣ የክላሲካል ሙዚቃ መፈጠርና፣ በተለይም በአሪስቶክራሲውና እያደገ በመጣው የከበርቴ መደብ ዘንድ መወደድ፣ የዕደ-ጥበብ ዕድገትና የንግድ መስፋፋት፣ አንድ ላይ በመጣመር ለአውሮፓ ዕድገት ልዩ ዕምርታን ሰጡት። ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ብቅ ብቅ ያሉት ህብረ-ብሄሮችና ፍጹም ሞናርኪያዊ አገዛዞች በውድድር ዓለም ውስጥ በመግባት ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ማካሄድ ጀመሩ። የህብረ-ብሄር ፈለግ ልዩ መልክ እየያዘ በመሄድ ህዝብን ማስተሳሰር ጀመረ።

        ነገሩን ለማሳጠር፣ በአጠቃላይ በተለይም ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ሬናሳንስን ተሻግሮ ከፍተኛ ምርምርና ስልጣኔ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ሊተከል የቻለው የግሪኩን የምርምር ዘዴ በመከተል ብቻ ነው። በአንድ በኩል የፕላቶንን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የአርስቲቶለስን በሚከተሉ መሀከል የተነሳውን የአመለካከት ግጭት ወደ ኋላ ብንተው የግሪኩን ስልጣኔ ሳይረዱ አንድን ህብረተሰብ መገንባት በፍጹም እንደማይቻል ነው። የብዙ አፍሪቃ አገሮችም ዋናው ችግር የስልጣኔን ምንጭንና የአእምሮንና የህሊናን ሚና በፍጹም ለመረዳት ያለመቻል ነው። በብዙ የአፍሪቃ አገሮች አገራችንንም ጨምሮ የሚታየው የተዘበራረቀ ሁኔታ የሚያረጋግጠው የግሪኩን ህዝብ አስተሳሰብ አስመልክቶ  በሆሜር እንደተደረሰው ዐይነት አእምሮና አካልን ለያይቶ በማየት የራስን ህይወት በራስ ለመወሰን ያለመቻልና ለጥበባዊ ስራ ታጥቆ አለመነሳት ነው። ወይም ደግሞ በአፍሪቃ ምድር ውስጥ አእምሮና መንፈስ ምን እንደሀኑ የሚታወቅ አይመስልም። ከዚህ በመነሳት ለምን እኛ አፍሪቃውን፣ በተለይም ኢትዮጵያኖች አስተሳሰባችን በተወሰነ ክልል ውስጥ ብቻ እንደሚሸከረከር አጠር ባለ መልክ እንቃኝ። ይህንን ስንረዳ ብቻ የኛንም ሆነ የገዢዎቻችንን ድርጊት በሚገባ መረዳት እንችላለን። ይህንን ሳይገነዘቡ ወደ ፊት የሚደረግ ሽምጠጣ የመጨረሻ መጨረሻ ጥፋት ውስጥ ነው የሚከተን። የአእምሮንና የመንፈስን ልዩ ቦታ ስንረዳ፣ ራሱ ዕውነተኛ ዕውቀት ማለት ምን ማለት እንደሆነም መገንዘብ እንችላለን። ይህ ብቻ ሲሆን፣ ዕውነተኛውን ዕውቀት ከአሳሳቹ መለየት እንችላለን። አእምሮንና መንፈስን ከፍተኛ ቦታ በመስጠትም ጥያቄ በማቅረብና ህብረተሰብአዊ ትችትን  እንደችግር መፈለጊያና መፍቺያ በማድረግ አንድ ጥሩ ውጤት ላይ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት ለማድረግ እንችላለን።

ለምን በእኛ ዘንድ የአስተሳሰብ ልዩነት ይፈጠራል?

                  በአንድ አካባቢ ተወልደን፣ በአንድ አካባቢ አድገንና አንድ ትምህርት ቤትም ሄደንና ተመሳሳይ ትምህርት ቀስመን በባህርያችንና በአካባቢያችን ያሉትን ነገሮች በመረዳት በመሀከላችን ልዩነቶች ይኖራሉ። ሌላው ቀርቶ ከአንድ እናትና አባት የተወለዱ ልጆች አንድ ዐይነት አስተዳደግ ኖሯቸውና ተመሳሳይ ምግብ በልተው አድገው በአስተሳሳባቸው ይለያያሉ። አንዱ ሞኝ ይሆናል፤ ሌላኛው ብልጥና ነገሮችን በቀላሉ የሚረዳ። አንደኛው የፖለቲካ ዝንባሌ ሲኖረው ሌላው ፖለቲካን የሚባል ነገር የሚርቅ ይሆናል። ለምን ይህ እንደሚሆን የሳይኮሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው ካልሆነ በስተቀር እንደኔ ያለ ሌላ ሙያ ያለው ሰው በቀላሉ ሊረዳው አይችልም። ይህንን በአስተሳሳብ መለያየት እንደፈጥሮአዊና ለህብረተሰብ አስፈላጊም ነው ብለን አምነን ብንቀበለውም፣ ወደ ትምህርት ገበታ ስነሰማራ እንደ የሁኔታው አይ በዚያው ጸንተን እንቆያለን፣ ወይም ደግሞ አዕምሮአችን ከአዲስ ሁኔታና ዕውቀት ጋር ሲገናኝ ቀድሞ የነበረው አስተሳሰብ እየተሞረደ ወይም እየተሻለ የሚመጣበት ሁኔታ አለ። በሌላ ወገን ደግሞ የትምህርቱ አሰጣጥና የአካባቢውም ሁኔታ የተበላሸ ከሆነ የሃሳብ ዝብርቅርቅነትና ነገሮችን በቀላሉ ያለመረዳት፣ የሃሳብ ሚዛናዊነት በጭንቅላት ውስጥ እንዳይዳብር የአንድ ታዳጊ ልጅ ጭንቅላት ቀጭጮ እንዲቀር የሚገደድበት ሁኔታ እንዳለ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። በሌላ አነጋገር ከቅድመ-ወሊድ በፊት በሚፈጠር ያልተስተካከለ ሁኔታ ወይም የአልክሆል ፍጆታ የአንድ ለወሊድ የተቃረበ ህጻን ጭንቅላት ካልተበረዘ በስተቀር አንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ የሚደረግለት እንክብካቤ ለአዕምሮ ዕድገቱ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት በሳይንቲሰቶች የተደረሰበት ድምዳሜ ነው። አሁንም በሌላ አነጋገር በአንድ ህጻን የኢንተለጀንስ ግንባታ ጂን የሚጫወተው ሚና 20 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ የአመጋገብና የአካባቢ እንዲሁም አጠቃላዩ የባህል ሁኔታ በአንድ ታዳጊ ልጅ ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው። በሰፊውና በጥልቀት ማሰብና አዳዲስ ሃሳቦች ማፍለቅ መቻልም ሆነ አለመቻል ከጠቅላላው ባህላዊ ክንውን ውጭ ተነጥለው በፍጹም ሊታዩ አይችሉም። ይህንን ለመረዳት አለመቻል ወይም ከቁም ነገር ውስጥ አለማስገባት ሀቁን የመፈለጉና ለስልጣኔ የሚደረገውን ትግል ከመጀመሪያወኑ እንዲጨናገፍ ያደርጋል።

        በብዙ ጥናቶች እንደተደረሰበት፣ በታሪክ ውስጥ ባህልና የባህል ዕድገት ከምግብ ጋር ተጨምሮ ለሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ዕድገትና በሰፊውና በጥልቀት ማሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ነው። የማንኛውም ሰው አስተሳሰብ ከባህልና ካለበት አካባቢና የቀን ተቀን ከሚያጋጥመውና ከሚለምደው ሁኔታ ተነጥሎ በፍጹም ሊታይ አይችልም። እንደ የማህበራዊ ሁኔታዎችና በአካባቢው ባለው ኢ-ፖለቲካዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንድ ሰው ለፖለቲካ ያለው ፍላጎትም ሆነ ፖለቲካን መጥላት በዚያው ባለበት ሁኔታ ይወሰናል ማለት ነው። ስለሆነም አንደኛው ተራማጅ፣ ሌላው አድሃሪ ወይም ለውጥ መኖር የለበትም ብሎ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት፣ ሌላው ደግሞ ከዚህ ሁሉ ዝባዝንኬ ርቆ የሚኖር አለ። ስለሆነም የሰዎችን የማሰብ ኃይል ከአካባቢና ከምግብ እንዲሁም ከአስተዳደግ ጋር አገናኝተን ለመግለጽ 㜎የምንችለውን ያህል፣ በሌላ ወገን ግን አንደኛው ለምን ዕድገትንና ለውጥን እንደሚፈልግ ሌላው ደግሞ ይህንን እንደሚቀናቀን መግልጽ የሚያሰቸግር ይመስለኛል። ከመጀመሪያውኑ ለውጥን የሚቀናቀኑ፣ አዲስ አስተሳሰብ በፈለቀ ቁጥር እንደመጥፎ ነገር የሚቆጥሩና በተቻለ መጠን እስከማጥፋት ድረስ እንደሚሄዱ በአገራችንም ሆነ በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ ነው። አንዳንድ ሰዎችን ወደ መጥፎ ስራ ምን ነገር እንደሚገፋፋቸው ሙሉ በሙሉ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በማህበርም ደረጃ ይደራጁ ወይም በተናጠል አንድ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ካለቸው ሌላ አስተሳሰብ ሲመጣ ተቃውሞ ያሳያሉ። የሌላው የኑሮ መሻሻል የነሱን የተሻለ የኑሮ ሁኔታ የሚጎዳ ይመስላቸውና አዲሱን አስተሳሰብ ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ በግራና በቀኞች መሀከል፣ ወይም በአንዳንዶች አባባል በአርቆ-አሳቢዎችና አርቀው-በማያስቡ መሀከል የሚደረግ ትግል ያስመስሉታል። ለስልጣኔ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚታገል ሁሉ አክራሪና አርቆ የማያስብ እየተባለ የማይሆን ስም ይሰጠዋል። ነገሩ፣ እነሱ የመሰረቱትን ወይም የሚፈልጉትን አስቀያሚ ስርዓት ዝም ብለህ ተቀበል፤ ጥያቄ አትጠይቅ፤ አትመራመርም እንደማለት ነው።

       እንደዚህ የተዘበራረቀ አስተሳሰብ በብዙዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ እንደሚላወስና አስተሳሰባችንና ድርጊታችንን እንደሚወስን መገመት ይቻል። ከአገርም ወጥተን በብዙዎች አስር ዐመታት በአውሮፓ ምድርና በአሜሪካ ብንኖርም አብዛኞቻችን የበለጠ በዘልማዳዊ አስተሳሰብ የታሰርን ነን። ያለንበት ሁኔታና ራስን ለማሸነፍ እዚህና እዚያ መፘፘጥ ለማሰብም ሆነ ለመመራመር ዕድል አይሰጠንም። በሌላ በኩል ደግሞ ለአገራችን ያለን ፍቅር በብዙዎቻችን ግንባር ላይ ሲነበብ ይታያል። ፍቅርና ፍላጎት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በዘልማዳዊ አስተሳሰብ ተከቦ ትግል ማካሄድና አንዳችም ውጤት ላይ መድረስ እንደማይቻል ቢያንስ ያለፈው ሃያ ዐመት ትግል ያረጋግጣል። በተጨማሪም በትክክል ምን እንደምንፈልግ ለማወቅ ግራ ስለተጋባን እንደየሁኔታው ሃሳቦቻችን ይለዋወጣሉ። በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ጥልቅ ከሚሉት ድርጅቶችም ሆነ ታዋቂ ከሚባሉ ግለሰቦች ከሚሰነዘርለን የትግል መፈክር ፕሮግራም በስተቀር እንደ አንድ ነጻነት እንዳለው ሰው በግለሰብ ጥረት ተነሳስተን የራሳችንን የትግል ፈለግ መከተል ያልቻልንና አንድ አጠቃላይ ርዕይ የሌለን በብዙ ሺህዎች የምንቆጠር ነን። ይህ ዐይነቱ ባህርይና አመለካከት ትላንት የነበረና ዛሬ ደግሞ በአዲስ መልክ የሚከታተለንና ህይወታችንን የሚፈታተነን፣ ለዕውነተኛው ነጻነት እንቅፋት የሆነ ነው ብል ምናልባት የምሳሳት አይደለሁም። ይህንን ለመረዳት ትንሽ ክሮኖሎጂካል በሆነ መልክ አጠር መጠን አድርገን እንመልከተው።

       ወደድንም ጠላንም ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ዘመናዊ ነው የሚባለው በአፄ ኃይለስላሴ የገባው ለውጥ ዝብርቅርቅነት ከመፍጠሩ በስተቀር፣ በተለይም በምሁሩ ዘንድ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የመንፈስ አድነትና ጥራት ሊያዳብር አላስቻለውም። በአንዳንድ ምሁራን ህብረተሰቡንና አስተዳደሩን የሚተቹ ጽሀፎች-ለምሳሌ ፍቅር እስከመቃብርንና አርአያን እንዲሁም የአቤ ጎበናን ጽሁፎች መመልከት ይቻላል-ሰፋ ያለ ምሁሩን ሊያቅፍና ወደ ተቀረውም የህብረተሰብ ክፍል ቀስ በቀስ ሊተላለፍ የሚችል ስራ ሊሰራ አልተቻለም። በአንዳንድ የነቁ ምሁራን እንደ ፋውስትና ሼክስፔር የመሳሰሉት ስነ-ጽሁፎችና የድራማ ስራዎች ወደ አማርኛ ቢተረጎሙና ቲአትርም ቢሰራባቸው፣ እንደ አንድ ከፍተኛ መብረቅ ያለውን ስርዓት የሚያናጉም አልነበሩም። በአብዛኛውም ዘንድ እንደቁም ነገርና እንደ አስተሳሰብ መለወጫ መሳሪያዎች ተደርገው አልተወሰዱም፤ ግንዛቤም አልነበረም። ስለሆነም፣ የግሪኩ ስልጣኔ ለአውሮፓው ዕድገት የቱን ያህል በር የከፈተና መሰረት የጣለ መሆኑን ግንዛቤ አልነበረም። በሃምሳኛው ዐመትና በስድሳኛው ዐመታት እንቅስቃሴ ሲጀምርና ሲፋፋም የግዴታ አንድ ወጥ አመለካከት ሊዳብር ችሏል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የተማሪውን እንቅስቃሴ ታሪክ ለተከታተለ፣ ውጭ አገር እንዲማሩ በተላኩ ኢትዮጵያውን ዘንድ የጥገና ለውጥ ነው የሚያስፈልገው በሚለውና ስርዓቱን እንዳለ መለወጥ ነው በሚለው መሀከል የጦፈ ክርክር እንደነበረና፣ የኋላ ኋላ የግራው እንቅስቃሴ በአሸናፊነት እንደወጣ መረዳት ይችላል። አሁንም፣ ከተማሪው ማህበር የታሪክ ማህደር መረዳት እንደሚቻለው፣ ከስድሳዎች ዐመታት አጋማሽ ጅምሮ በዓለም አቀፍ ዙሪያ የተካሄደው ፀረ-ኤምፔያሊስት ትግልም ይበልጥ በአቋሙ እንዲገፋበት እንደረዳውና ከዚህም ሌላ አማራጭ የትግል ስልትና የግራ ቲዎሪ በስተቀር እንዳልነበረ ነው። በተለይም እ.አ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በድሮው የምዕራብ ጀርመንና በፈረንሳይ አገር የተማሪ እንቅስቃሴ ማየልና መስፋፋት የግዴታ ለኢትዮጵያ የተማሪዎች ማህበር እንቅስቃሴ በአቋሙ እንዲጸናበት እንደረዳው መገንዘብ ይቻላል። አዝማሚያውም ይህ ዐይነት ስለነበር አንድን ትውልድ ለምን ይህንን ተከተልክ ብሎ መወንጀል ትክክል አይደለም። ራሱ የአገሪቱ ሁኔታና ጠበብ ብሎ የቀረበው የትምህርት አሰጣጥና ዓለም አቀፋዊው ሁኔታ የሰውን አመለካከት ወደዚህ የሚገፉ ነበሩ። የተማሪውን እንቅስቃሴ የሚያስከስሰው አውቆም ሆነ ባለማወቅ ልዩ ልዩ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በሰፊው አንስቶ ከመወያየትና ከመከራከር ይልቅ የክርክሩን መድረክ እያጠበበው መምጣቱ ነው። በተለይም ከ1940ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ጀምሮ ቀስ በቀስ እያለ ያደገውንም ሆነ እየተዘበራረቀ የመጣውን ህብረተሰብና የህብረተሰብ ኃይል ከህብረተሰብ ሳይንስና ከባህልም ሆነ ከህሊና ሳይንስ አንጻር በመገምገም ከፖለቲካ ስትራቴጂ አንፃር ምን ምን እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ሊገነዘብ አልቻልም። በህብረተሰብአችን ውስጥ በጊዜው የተፈጠረውን ህብረተሰብአዊ ውስጠ-ኃይል ሊረዳ የቻለ እንቅስቃሴ አልነበረም። በመሆኑም የደረሰበት ድምደማ የህብረተሰቡን ችግር በዕውቀት መሆኑ ቀርቶ በአመጽ እንደሚፈታ አመነ። ለምሳሌ በጊዜው በተማሪው እንቅስቃሴ፣ መንቃት ፣ መደራጀትና መታጠቅ የሚለውን መፈክር ለተመለከተ፣ እንቅስቃሴው በእርግጥም በዕውቀት ላይ ለተመሰረተ ህብረተሰብአዊ ግንባታ የማያመች እንደነበረ ነው። ለአንድ ህብረተሰብ በተለያዩ መስኮች መደራጀትና መንቃት አስፈላጊ ቢሆንም፣ የፖለቲካው ጥያቄ በማየሉ ሁሉም ነገር በዚህ ብቻ እንዲሸከርከር ለማድረግ በቃ። ንቃት የሚለውንም መፈክር ስንመለከት እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን እንዲያውቅና ከሌላው ጋር በመተባበርና በመተጋገዝ አገር በጋራ እንዲገነባ የሚያደርግ ሳይሆን፣ ህብረተሰቡን በጠላትና በወዳጅ መሀከል ከፋፍሎ እንዲያይ የሚያደርግ መፈክር ነበር። ለስራና ለፈጠራ በር የከፈተ ከመሆኑ ይልቅ ብዙ ተረበኞችንና የፖለቲካ አሉባልተኞች ብቅ እንዲሉ ያደረገ ነው። ከዚህም በመነሳት የብሄረ-ሰብ ጭቆናና ኢትዮጵያ የብሄረ-ሰቦች እስር ቤት ነች የሚለው ጎልቶ በመውጣት ብዙዎችን ሊያሳስት በቅቷል። በተጨማሪም ማርክሲዝምን እጅግ በጠባብ ጎኑ መመልከትና፣ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከማርክሲዝም አኳያ በተለያዩ መልኮች የተተነተኑትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ አለማስገባት የትግሉን አቅጣጫ ሊወስን ችሏል። ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳያመች በሩ የተዘጋ ነበር። ይህ ማለት ግን ምሁሮች አልነበሩም ማለት አይደለም። የኋላ ኋላ ደግሞ ጠቅላላው ትግል ሌላ አስተሳሰብ ያላቸውን በውይይትና በክርክር ማሳመን ቀርቶ በወዳጅና በጠላት መሀከል ከልሎ ለተለያዩ አስተሳሰቦች ክፍት አለማድረግ፣ ለማዳመጥና ለመደማመጥ አለመቻል፣ ትንሽ ዕውቀት የነበረውን መናቅና ማግለል፣ እነዚህ ሁኔታዎች ከነበሩን ከህብረተሰባችን ከቀሰምናቸውና ካደግንባቸው ባህል ጋር ተደምሮ የትግሉን አቅጣጫ ሊወስን ችሏል። በተጨማሪም፣ የሚነሱ ጥያቄዎችንም ሆነ አፍጠው አግጠው የሚታዩትን ችግሮች በክርክርና በውይይት ከመፍታት ይልቅ በአመጽ ለመፍታት መሞከር የህብረተሰብአችንን ችግር የባሰ ውስብስብ አደረገው። ችግርን በውይይትና በክርክር ለመፍታት የመቻል ባህል አለመኖር ደግሞ ከውስጥ ሆነው የራሳቸውን ህልም ለሚያልሙና፣ ብሄራዊ ባህርይና የመንፈስ አንድነትን አዳብሮ ለአንድ ዓላማ መታገልን ለማይፈልጉ ኃይሎች በሩን ከፈተላቸው። እጅግ በጠባብ አስተሳሰብ ጭንቅላቱ የተናወጠው የኤርትራ ነጻ አውጭ የሚባለው እንቅስቃሴ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚለው እምብዛም የምሁር መሰረት የሌለው እንቅስቃሴና፣ የትግሬ ነጻ አውጭ ነኝ ብሎ እዚህና እዚያ ይፘፘጥ የነበረውና ዛሬ በምሁራዊ ዕወቀት አልባነቱን  ያጋለጠው፣ ይህንን ዐይነቱን ቀዳዳና የተወሳሰበ ሁኔታ በመመልከት፣ ጠቅላላውን ትግል ወደ ጦር ትግል እንዲያመራ አደረጉ። ነጻነትን ከዕውነተኛ ዕውቀት፣ ከመንፈስና ከባህላዊ ተሃድሶ ነጥሎ በመመልከት የወጣቱንም አስተሳሰብ በአመጽ ዙሪያ እንዲሸከረከር በማድረግ ችግሩ እንዲባባስ ሆነ። ዕውነተኛ ስልጣኔ በሃሳብ ኃይል ብቻ ይገኛል የሚለው የተቀደስ አስተሳሰብ ቀርቶ፣ ድል  በጦርነት፣ በመጨፋጨፍና ወንድምን ገድሎ ጀግና ተብሎ በመጠራት ይገኛል ወደሚለው በመቀየሩ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣትና ህዝብ በከንቱ ደሙን አፈሰሰ። የኑሮ ትርጉምን፣ የህብረተሰብ ምንነትና፣ የቤተሰብ መመስረትን አስፈላጊነት በሚገባ ያልተገነዘበውና የነጻነትን ትርጉም ያጣመመው የብሄረ-ሰብ እንቅስቃሴ ሁሉ ራሱን ከሌላው በመለየትና፣ የሌላው ጥያቄና ችግር እኔን አያገባኝም በማለት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሳሳተ። ኑሮአቸውን አጨለመ። ይህም የሆሜሩን የግሪክ ዘመን ታሪክ ያስታውሰናል።

       ይህ ዐይነቱ በአመጽ ላይ የተደገፈ ትግል ከ1950ዎቹ ጀምሮ በማደግ ላይ የነበረውን የንዑስና ቀስ በቀስም ወደ ከበርቴያዊነት ሊለወጥ የሚችለውን የህብረተሰብ ክፍል ክፉኛ መታው። በራሱ ጥረትና ትግል ሀብት ያፈራና ቤተሰብ መስርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኝ የነበረ የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ እንደጠላት እየታየ አንዳንዱ ሲገደል፣ ሌላው ደግሞ ከነበረበት ቦታ በመሸሽ ተበታተነ። ይህ ሁኔታ በራሱ በተወሰኑ አካባቢዎች እየተረጋጋ የመጣውን ህብረተሰብ በመምታቱና ብዙ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነቶችን በመበጣጠሳቸው ድሮ ይታይ  የነበረው ዐይነት ህብረተሰብአዊ ውስጠ-ኃይል እንደገና በአዲሰ መልክ ብቅ ሊል አልቻለም። በየአካባቢዎች የህብረተሰቡ ምሰሶና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ሊፈጠሩ አልቻሉም። በአንጻሩ ግን በተለይም በአብዮቱ የመጨረሻ ወቅት ከህብረተሰብአዊ እሴት ይልቅ ጋጠ-ወጥነት እያየለ በመምጣቱ ህብረተሰቡ እንዳለ ተናጋ። ኢኮኖሚያዊ የስራ ክፍፍል፣ ባህላዊ ቅንጅቶችና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት ከማበብ ፈንታ፣ ህብረተሰቡን የሚሸረሽርና የሚያናጋ ኃይል እዚህና እዚያ ብቅ በማለቱ በተለይም አቅም የሌለውና ዕርዳታ የሚፈልገው የህብረተሰብ  ክፍል በሀዘን እንዲጨማደድ ተደረገ። ቂም በቀልነት፣ ጋጠ-ወጥነትና ህብረተሰብአዊ እሴት አለመኖር፣ በተለይም የካድሬው መለያ ሆኑ።㗹ስለሆነም በአፄው ዘመን ከነበረዉ ሀኔታ ጋር በመደመር ጠቅላላው አብዮታዊ ሂደት በአገራችን ምድር የነጻነትንና የስልጣኔን አርማ አንስቶ ለመታገል የሚችል ኃይል ብቅ እንዳይል አደረገ። በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ፣ መጠቋቆምና መገዳደል በህብረተሰብ ውስጥ ፍርሃትን አስከተለ። ከደርግ አገዛዝ መበታተንና ከነጻ ገበያ ተግባራዊ መሆን ጀምሮ አዲስ ሁኔታ በመፈጠሩ ሰፋ ላለ ህብረተሰብአዊ ግንባታ የሚደረገው ትግል ተሟጦ አለቀ። በተሳሳተ መልክ ይተረጎም የነበረው የነጻ ገበያ መፈክር ከፈጣሪነት ይልቅ ወደ ዘራፊነት የሚያመራን ሁኔታ ፈጠረ። ስግብግብነት፣ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ሀብትን ማፍራትና በሀብት መባለግ የተረፉትን ህብረተሰብአዊ እሴቶች ደመሰሳቸው። ስለሆነም ህብረተሰብአችን የጉልበተኞችና የአጉል ባለሀብቶች መፈንጫ መድረክ ሆነ። ህብረተሰቡ ዓላማ የሌለውና ለወጣቱም ትውልድ መጥፎ አርአያ የሆነን ሁኔታ ፈጠረ። ዕውነተኛ ዕውቀት ባልተስፋፋበት፣ የነቃና በጥሩ ባህል የታጠቀ የህብረተሰብ ክፍል በሌለበት አገር አጉል ተመጻዳቆች ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር በሌሎች ደካማ አገሮች የሚያደርሱትም የተበላሸና አገር አፍራሽ ሁኔታ በአገራችን ምድር በአሸናፊነት በመውጣት ሰፊው ህዝብ ተሸማቆ እንዲኖር ያሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ዛሬ ይህንን አስቸጋሪና አገር አፍራሽ ሁኔታ ለመቋቋም የሚችል ኃይል የለም። ሁሉም በነጻ ገበያ ስም ከመማል በስተቀር የስልጣኔን ሰፊ ትርጉም በመረዳት ለተቀደሰና ለረዥም ጌዜ ዓላማ ቆርጦ ለመነሳት የተዘጋጀ የህብረተሰብ ክፍል በባትሪም ፈልጎ ማግኘት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥፘል ማለት ይቻላል።

       በተማሪው እንቅስቃሴ ላይ የሚደረገውን ከታሪክ፣ ከህብረተሰብ መዘበራረቅ ተነጥሎ የሚወሰደውንና የሚሰነዘረውን ታሪከ-ቢሰ ትንተናና፣ ማን ነው ተጠያቂው? የሚለውን የማያስፈልገውን ውንጀላ ወደ ጎን ትተን-ለሳይንስና ለስልጣኔ የሚበጅ የትግል የትንተና ስላልሆነ- ወደድንም ጠላንም ሁለቱ የሚታወቁት እንቅስቃሴዎች ብሄራዊ ባህርይ እንደነበራቸው ነው። ይሁንና ግን፣ የመጨረሻ ውጤቱ የተቃራኒው ሆነ። ሶክራተስም እንደሚለው አንድ ሰው የሚሳሳተው ወይም የሚያጠፋው ሆን ብሎ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ለስህተት መፈጸም ዋናው ምክንያት አንድም አለማወቅ፣ ወይም ዕውቀት ቢኖር እንኳ ለማሰብ ፋታ ሊገኝ የማይችልበት ሁኔታ በሚፈጠርበት ወቅት ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ሰው መቶ በመቶ አርቆ-አሳቢ(Rational) ሊሆን አይችልም። ወይም ደግሞ በአንዳች ምክንያት ከቁጥጥር ውጭ የሚወጣበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ፣ ታላቁ ፑሽኪን በጣም አርቆ-አሳቢ ብቻ ሳይሆን በሊትሬቸር ስራውና በግጥሙ በጣም የታወቀና ለራሺያም ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዎ ያደረገ ሰው ነው። ይሁንና ግን የቤተ-መንግስት መሳፍንቶች በዕወቀቱ ስለሚቀኑበት ያበሸቁት ስለነበር በመጨረሻ ላይ ግን ራሱን መቆጣጣር ስላልቻለ ከአንዱ መስፍን ጋር ትግል እንጋጠም ብሎ፣ በአርባ ዐመቱ ህይወቱ ተቀጨ። እንደዚህ ዐይነት ቶሎ የሚከሰት የአጭር ጊዜ አርቆ-አላሳቢነት በሁላችንም ዘንድ ሊታይ ቢችልም፣ ይህ ዐይነቱ ባህርይ ስር የሰደደ ከሆነና ከግለሰቦች አልፎ ወደ ድርጅቶችና ወደ ታዳጊ ትውልድ ልክ እንደ ወረርሸኝ በሽታ ከተላለፈ እንደ ነቀርሳ በሽታ አንድን ህብረተሰብ በመገዝገዝ መጨረሻ ላይ ህብረተሰቡ አቅድ እንዲያጣና ተስፋ እንዲቆርጥ ይደረጋል። የሚገርመው ነገር ደግሞ ይህ ዐይነቱ የእልክ ጉዞ የሚያይለውና ዘለዓለሙን የሙጥኝ ብሎ የሚይዘው ትንሸ ፊደል ቀመስን የሚሉትን ነው። ባለፉት አርባ ዐመታት በአገራችንና በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ኤሊት በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚታይ መጥፎ በሽታ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ስህተት ሰራሁ ብሎ በድፍረት ለመናገር አለመፈለግ ወይም አለመቻልና ከስህተት ለመማር አለመፈለግ የአገራችንም ሆነ የብዙ ሶሰተኛው ዓለም አገር ኤሊቶች ባህል ሊሆን ችሏል። ለምሳሌ በአብዮቱ ወቅት ስለተሰራው ወንጀልና ስህተት ከመንግስትም ሆነ ተራማጅ ነን ከሚሉትና በእንቅስቃሴው ውስጥ ከተሳተፉት ድርጅቶች የሚሰጠው ትንተና በጣም አሳዛኝና አስቂኝ ነው። ሁሉም ተበዳይና መስዋዕትነትን የከፈለ እንጂ፣ በዚያ አገር ውስጥ ማንኛውም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተነሳስቶ ጥፋት ያጠፋ እንደሌለ ነው የሚነገረን።

       ያም ሆነ ይህ የተማሪው እንቅስቃሴ ማየል የአገራችን የህብረተሰብና ኢኮኖሚ ዕድገት ነጸብራቅ ነው። በዘመናዊነት የገባው የዕድገት ፈለግ አዲስ የኢኮኖሚና የባህል እንዲሁም የፖለቲካ ኃይል ብቅ ብሎ እንዲወጣና ፊዩዳላዊ አገዛዙንና የባህላዊ መሰረቱን እንዲቀናቀን የሚያስችል አልነበረም። የኢኮኖሚው ውስጠ-ኃይል ውስን በመሆኑ ከነጋዴ የህብረተሰብ ክፍልና እጅግ ከተዘበራረቀ ንዑስ ከበርቴ የህብረተሰብ ክፍል በስተቀር ዕድገትን በቴክኖሎጂ መሰረት ላይ ያደረገ የኢንዱስትሪ ከበርቴ ብቅ ሊል አልቻለም። አገዛዙ ከሚከተለው እጅግ የተወላገደ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የውጭው ኃይል ግፊት ተደምሮበት ለአዲስ ብሄራዊ ከበርቴ መደብ ብቅ ማለትና መዳበር መፈናፈኛ ሊሰጥ አልቻለም። በየክፍለ ሀገሩም የተዘረጉት ኢንስቲቱሸኖች በሙሉ ለዕድገት የሚያመቹ ስላልነበሩ ህብረተሰቡ በዚያው ቀጭጮ እንዲቀር የማድረግ ኃይላቸው ከፍተኛ ነበር። የከተማዎች በዕቅድ አለመሰራት፣ ስርዓት ያላቸው የስራ መስኮች አለመኖርና ሰፋ ያለ ባህላዊ እንቅስቃሴ ያለመዳበር ወይም ያለመገኘት የሰፊውን ህዝብ ሆነ ተማርኩ የሚለውን አስተሳሰብና ድርጊት ሊወስኑ ችለዋል።  በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የተማሪው እንቅስቃሴ ብቅ ሊልና ጎልቶ መታየትም የጀመረው። የተማሪውም እንቅስቃሴ በሁኔታዎች በመሳሳትም ሆነ ለማውጣትና ለማውረድ ፋታ ባለማግኘት ሚናውን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ እንዲያይ አድርጎታል። ዛሬ በዚህ መልክ ሲጻፍም ሆነ ሲታይ “የትግል ልምድ ያላቸውና” እህቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን ያጡ፣ ይህ ደግሞ የማያውቀውን ነው ዝም ብሎ የሚዘላብደው ሊሉ ይችሉ ይሆናል። በስልጣኔና በለውጥ የምናምን ከሆነ እያንዳንዱ ተከታይ ትውልድ ያለፈውን ታሪክ ከብዙ አቅጣጫዎች ለመገምገም መቻል አለበት። የነበሩንና ያሉንን ድክመቶችና መልካም ጎኖች አንስተን የማንወያይ ከሆነ ደግሞ በፍጹም መሻሻል አንችልም። ዕድገትም ሊኖር አይችልም። ስለዚህም እዚህ ላይ በዚህ መልክ ሲተነተን የተማሪውን እንቅስቃሴ እንዲያው በደፈናው ለመወንጀል ሳይሆን፣ በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንደተፈጠረና ይህንን ዐይነቱን የትግል ፈለግ ለመከተል ምን እንዳስገደደው እኔ በምረዳው መልክ ለማቅረብ ብቻ ነው። ተሳስተሀል የሚሉ ካሉ በነጻ ዓለም ውስጥ ስለ።ምንኖር የዚህን ግለሰብ ትንተና የመተቸትና አስተያተቻውን የመሰንዘር መብት አላቸው።

       ይሁንና ግን የተማሪው እንቅስቃሴ የማርክሲዝምን-ሌኒነዝምን አርማ አንግቦ ለተወሰነ ዐመታት ከታገለ በኋላ እንቅስቃሴው እየተዳከመ ሲሄድ ቲዎሪውን እርግፍ አደርጎ ወደ መጣል ደረሰ። በመጀመሪያ ለጥቂት ምሁራን የማርክሲስት ቲዎሪ ግልጽ የሆነውን ያህል ለአብዛኛው ህዝብና ለተከታዮቻቸው ግልጽ አልነበረም። የተወሳሰበው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር በዚህ ቲዎሪ ሊፈታ ይችላል የሚል በሰፊው ተተንትኖ የቀረበ ጥናት አልነበረም። አብዛኛውን ጊዜ ይካሄድ የነበረው ክርክር እንካ ስላንቲሃን ያስቀደመ እንጂ ሳይንሳዊ ፈለግን በማስቀደም የህብረተሰባችንን የተወሳሳበ ችግር በየደረጃው በዚህ መልክና በዚህኛው ፖሊሲ አማካይነት ሊፈታ ይችላል ተብሎ ክርክርና ውይይት የሚካሄድበት ሁኔታ ሊፈጠር አልቻለም። ይህም የሚያሳየው በጊዜው የነበረውን ተማሪውን እንቅስቃሴ ውስንነትና የባህል ችግር እንዳለ ነው። ትግሎ ካከሰመና የወታደሩ አገዛዝ ከተደላደለ በኋላ የተያዘው ፈሊጥ ቲዎሪውን እርግፍ አድርጎ በመጣል የተጠማዘዘ ጉዞ በመጓዝ ሳያውቁ ለትገሉ እንቅፋት የሆነ ሁኔታን መፍጠር ነበር። አቋምን መቀያየርና በየጊዜው አዳዲስ ፕሮግራምን ማውጣት የሚያመለክተው ከተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ብቅ ያሉት ድርጅቶች ምን ያህል ችግር እንደነበረባቸው ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ቲዎሪውን እርግፍ አድርጎ ሲተው ለምን በቀድሞው መልክ መታገል እንደማይቻል በትንተና መልክ የቀረበ ሰፋ ያለ ትንተና ሊቀርብ አልቻለም። አንዳንዶቹ የሶሻል ዲሞክረቲክን አቋም ይዘናል ቢሉም ለምን ይህንን መያዝ እንደተገደዱና በዚህ መልክስ የአገራችንን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የባህል ችግሮች መፍታት እንደሚችሉ አላማከቱም። ይህ ዐይነቱ ችግር የእነዚህ ድርጅቶች ችግር ብቻ ሳይሆን የኋላ ኋላ የሊበራል ዲሞክራቲን ስምን ይዘው የወጡ ድርጅቶች ችግር ነው። የአንድ ህብረተሰብ ችግር በስም መለዋወጥና እንደዚህ ነኝ ብሎ በመጥራት የሚፈታ ይመስል ብዙዎች ብሄራዊ ባህርይ አለን የሚሉ ድርጅቶች ይህንን ሆነ ወይም ያኛውን ስም መያዝ ተገደዱ። በዚህ አቋማቸው ይመኑበት እንደሆን እየተነተኑ ሊያስተምሩንና ሊያስረዱን አልቻሉም። አንድ ማለት የሚቻል ነገር የድርጅቶችን ታሪክና ስም ለተከታተለ በብዙ ፈተና ከታች ወደ ላይ እየተጣሩና እየተፈተኑ ወደ ላይ የወጡ አይደሉም። የአገራችን የተዘበራረቀና የተወላገደ ሁኔታ የወለዳቸውና ጊዜያዊውን ሁኔታ በመጠቀም ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚታገሉ ነው የሚያስመስላቸው።

       ስለሆነም በዛሬው አገዛዝ ባለፉት 20 ዓመታት ተግባራዊ የሆኑትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች እንዲሁም አጠቃላዩን ፖለቲካ ደረጃ በደረጃ በመከታተል ለምን እንደሚቃወሙና ለምንስ ዓላማ እንደሚታገሉ አላሳዩንም። በተለይም በአገዛዙ ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመተቸት ይህ ፖሊሲ ለምን ድህነትን በከፋ መልክ እንዲበራከት እንዳደረገ አማራጭ መፍትሄ ሊያቀርቡ አልቻሉም። አንዳንዶቹ የጠጨባጩን ሁኔታ ከማንበብ ይልቅ በስሜት ብቻ በመገፋፋት አገዛዙ የሚከተለው ፖሊሲ የማርክሲስት ኢኮኖሚ ፖሊሲና አብዮታዊ ዲሞክራሲዊ ፖሊሲ ነው በማለት ወደ ውዥንብር መንዛት ተሸጋግረዋል።

        ለብሄረ-ሰቦቻቸው ነጻነት እስከመገንጠል ደረጃ ድረስ እንታገላለን የሚሉትን ብንወስድ ደግሞ በምንም ዐይነት የሳይንስ መከራከሪያ ዘዴ ሊያምኑ አይችሉም። አይፈልጉምም። አስተሳሰባቸው ሁሉ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ ከጥበብና ከፍልስፍና፣ እንዲሁም ለአንድ ህብረተሰብ አስፈላጊ ከሆኑ ዕውቀቶች ውጭ ትግላቸውን ስለሚመለከቱና ስለሚሸከረከሩ ሰፋ ላለ ስልጣኔ ብንታገል ይሻላል ብሎ በፎርሙላ መልክ እንኳ ቢቀርብላቸው በፍጹም አይቀበሉም። ይህ የሃሳብ ግትርነታቸውና ዘለዓለማዊ ጥርጣሬያቸው ለአንድ ህብረተሰብ የሚደረገውን ጠቅላላውን ህዝብ የሚመለከት የስልጣኔ ፈለግ እያጨለመው መጥቷል ማለት ይቻላል። ይህ የትግል ዘዴያቸው ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ ራሳቸውንም እንደሚያጠፋና፣ እንታገልለታለን ለሚሉት ህዝብ ዘለዓለማዊ ጠንቅ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ሳይንሰ-አልባና የፍልስፍና መሰረት የሌለው ትግል የሚያመረቃ ውጤት ለማምጣት የማያስችል ስለሆነ ነው። ነገሩን ይበልጥ ለመረዳት፣ ሁለቱ የብሄረ-ሰብ ነጻ አውጭ ነበርን በሚሉትና አሁን ወደ መንግስትነት በተለወጡትና፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚለውን የትግል ዘዴዎችና አደገኛነት ጠጋ ብለን እንመልከት። የሶስቱም ድርጅቶች መሪዎች የማይሆን መፈክር አንግበው በመነሳት በወጣቱ ጭንቅላት ውስጥ ስርጎ በመግባትና የአስተሳሰብ አድማሱን በማጥበብ ካለምንም ፍርሃት ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተቀራርቦ እንዳይወያይ መሰናክል እንደፈጠሩበት የታወቀ ጉዳይ ነው። ይህንን ችግር መፍታት ስንችልና የተለያየ ብሄረ-ሰብ አባል ነን የሚሉ ግለሰቦች ከተተበተቡበት አጉል የድንቁርና ሰንሰለት ሲላቀቁ ብቻ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚስማማ አገር መገንባት ይቻላል። ጥርጣሬ ባለበት፣ ጥያቄ በማይጠየቅበትና የሃሳብ መንሸራሸር በማይኖርበት ሁኔታ ውስጥ ለጋራ ዓላማ መታገል በጣም አስቸጋሪ ነው።

        የኤርትራን ነጻ አውጭ ድርጅትና(EPLF)  የኤርትራውያንን አስተሳሰብ ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ እንመልከት። በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን በኤርትራ ህዝብ ላይ ስህተትና በደል እንደተፈጸመ የማይካደ ሀቅ ነው። ይሁንና ግን፣ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተፈጸመው በደል ከጠቅላላው የአገሪቱ ወደ ኋላ-መቅረትና የአፄው መንግስት ከሚከተለው አጠቃላይ ፖለቲካ ተነጥሎ ሊታይ በፍጹም የሚችል አይደለም። በጊዜው አፄው ለኤርትራውያን ዲሞክራት፣ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ተቃራኒውን ሊያደርጉ አይችሉም ነበር። ፊዩዳላዊ አመለካከታቸውና ከጣሊያን መሸነፍና መባረር በኋላ ያዋቀሩት አገዛዝ በተወሰነ ክልል ብቻ ነው እንዲያስቡ ያስገደዳቸው። ኤርትራውያንም ሆኑ ሌሎች የነጻ አውጭ ነን የሚሉት ድርጅቶች ይህንን በኢትዮጵያ ውስጥ ለዕድገትና ሰፋ ላለ ስልጣኔ እንቅፋት ሆኖ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሰንሰለት ነው ሊገነዘቡ ያልቻሉት። ይህም ሊሆን የቻለው፣ ሺለር እንደሚያስተምረን ነገሮችን በጣጥሰው ስለሚመለከቱና ራሳችውም በፈጠሩት፣ አብዛኛውን ጊዜ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ሊጣጣም የማይችል አስተሳሰብ የትግል መመሪያቸው ስላደረጉና ዛሬም ስለሚከተሉ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያልተጠናቀቀው የህብረ-ብሄር አገዛዝ ምስረታ ከየብሄረ-ሰቡ የወጣውን ኤሊት ነኝ ባይ ዕውነተኛ ነጻነት ፈላጊ መሆኑ ቀርቶ፣ ተበዳይነትን አጉልቶ በማሳየት እኔም ስልጣን ይገባኛል ወይም ተገንጥዬ ሄዳለሁ የሚለውን መፈክር ወደ ውጭ አውጥቶ እንዲታገል አስገድዶታል። በብዙዎቹ ዘንድ ያልነበረውና ያለው የግንዛቤ ችግር በዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነጻነትና በብሄረ-ረሰቦች ነጻነት መሀከል ያለው ዲያሌክቲካዊ ትግል ተሳስሮ ለመታየት ያለመቻሉ ነው። ይህ ነገሮችን ገነጣጥሎና በጠባቡ መመልከት ወደ ባሰ መሰሪህነትና እልክ ወደሚያሲዝ ትግል እያመራ መጣ። ትግሉ በምንም ዐይነት፣ በየትኛውም የሳይንስ መነጽር ቢታይ ለዕውነተኛ ነጻነት የሚያመች አይደለም። የተለያዩ ብሄረ-ሰብ አባላትን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ የሚያደርግና የኑሮን ትርጉም መሪዎቻቸው በተረጎሙላቸውና በነደፉላቸው የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ ብቻ እንዲሽከረከር ከማድረጉ በስተቀር።

       ስለሆነም የኤርትራው ነጻ አውጭ ድርጅት ለሌሎችም ምሳሌ በመሆን፣ በአንድ በኩል ከውስጥ እንደ ነቀርሳ በሽታ መሰርሰር፣ ከውጭ ደግሞ ርዳታ በማግኘት የደፈጣ ውጊያ ማድረግና ጠቅላላውን ህብረሰተብ ማናጋት እንደሙያ አድርጎ ተያያዘው። የትግሉ ፈሊጥ አንድ ቤት በመሰራት ላይ እያለ ወይም ከተሰራ በኋላ እሱን አፈራርሶ በተበላሸ መልክ እንደገና እገነባዋለሁ እንደማለት የሚቆጠር ከተጣመመ አስተሳሰብ የመነጨ ነው። ይህ እልከኝነት የተሞላበት ትግል ወደ ውስጥ ወጣቱን በማዳረስና ተደላድሎ የሚኖራውን፣ በአንዳንዶች በተሰሳሳተ መልክ ሚድል ክላስ ተብሎ የሚጠራውን ኤርትራዊ ሁሉ በማዳረስ አገዛዙን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚገዘግዝ ሆነ። አዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍለ-ሀገሮች ተወልዶ፣ ከሌሎች ብሄረ-ሰቦች ጋር ጭቃ እያቦካ አድጎና ትምህርት ቤት ሄዶ በተነሰነሰው የጥላቻ መርዝ ኢትዮጵያውነቱን መካድና ለኤርትራ ብቻ ፍቅር ማሳደር ጀመረ። ለማንኛውም ሰው የተወለደበትና ያደገበት፣ እንዲሁም ጫካም ሄዶ ተራራ ላይ ወጥቶ ብዙ ነገር ያያበትን ነው እንጂ ፍቅር የሚያሳድርበት፣ ያልተወለደበትና ያላደገበት እንዴት አድርጎ ፍቅር ሊያሳድርበት ይችላል? የማይገባኝ የህሊና አወቃቀርና በምንም ሳይንስ የማይደገፍ “የብሄረተኝነት ስሜት” ነው።  ያም ሆነ ይህ አብዛኛው በመሳሳት “የበላበትን ወጪት ሰባሪ” እንዲሉ፣ ቢበደሉም እንኳ እስከዚህ ድረስ የከረረ አቋም መወሰድ አይገባቸውም ነበር። ግን ደግሞ ጭንቅላት ሲታወር፣ የማመዛዘን ኃይል ተሟጦ ሲያልቅ ከአውሬነት በታች ባህርይ የሚይዝ ብዙ ሰው አለ። በወታደር መዋቅርና በስለላ ድርጅት ውስጥ አልፎ በከፊል በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትንና በንግድ የተሰማሩትን አንዳንድ ኤርትራውያንን በማካተት፣ ኤርትራውያንን እንደህብረተሰቡ አካልና ለዕድገት የቆሙ ሳይሆኑ ለጊዜያዊ ጥቅም የተቀመጡና አንድ ቀን ኤርትራ ነጻ ስትወጣ ጓዛቸውን ጠቅለለው የሚሄዱ ነበር የሚያስመስላቸው። ይህ ችግር የመነጨውና ዛሬም በብዙዎቹ መንፈስ ተንጠልጥሎ የቀረው፣ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ አናሳ ብሄረሰቦች ቢኖሩም፣ በንፅፅራዊ መልክ ሲታይ ያልተቀላቀለና በህበረተሰቡ ውስጥ የሃሳብ መሽከርከር ያልዳበረበት በመሆኑ ነው። ከሌሎች ክፍለ ሀገሮች በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭቆናና አመለካከት የኢጣሊያኑ ስድሳ ዐመት ካፒታሊዝም ባህላዊ ተሃድሶ እንዳላመጣ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት፣ በኢጣሊያን የቅኝ አገዛዝ ስር ስድሳ ዐመት ያህል መቆየት ስልጣኔን ያላበሰ ሳይሆን፣ በዕውነተኛ ስልጣኔ የማይለካን ጉራንና ከሌላው እንበልጣልን የሚለውን አስተሳሰብ በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል በጭንቅላቱ ውስጥ እንዲተከል ነው ያደረገው። ቱካዳይስ የሚባለው ከሄሬዶተስ ቀጥሎ የነበረው ሰብአዊው የታሪክ ጸሀፊ እንደዚህ ዐይነቱን ጉራ ፕራውድ አሮጋንሲ(Proud Arrogancy)  ብሎ ይጠራዋል። ግለሰቦች ራሳቸውን ካለወቁና የሌላውን ሰው መብት ካላረጋገጡና ሌላውንም በንቀት የሚመለከቱ ከሆነ ለራሳቸውም ነጻነት ሆነ ላሉበት ህብረተሰብ ዘለዓለማዊ ጠንቅ ሆነው ነው የሚቀሩት። አሰቸጋሪው ጉዳይ በአንድ በኩል የተለየሁ ነኝ፣ በታሪክም ሆነ በባህል የሚያገናኘን  የለም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከናንተ ጭንቅላት ላይ አንወድቅም የሚለው አስተሳሰብ ጤናማ ስርዓት ለመመስረት አያስችልም። ይህ ዐይነቱ በአንድ በኩል ነጻነቴን እወቁልኝ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከናንተ ጭንቅላት ላይ አልወርድም ማለት በአጉል የፖለቲካ ስሌት ሲታይ የበላይነትን እንቀዳጅ ማለት ነው። ይህ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ደግሞ በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን ሊሰራ በፍጹም አይችልም።

       ያም ሆነ ይህ፣ ኤርትራውያን ከባርነት ይልቅ ነጻነትን እንመርጣለን ብለው የራሳቸውን መንግስት ከመሰረቱ በኋላ ገነት ሳይሆን የሲኦል አገዛዝ ነው የጠበቃቸው። መራብና መሰደድ እንዲሁም መንገላታት ነው እጣቸው የሆነው። አሁንም ቢሆን በአብዛኛዎቹ ጭንቅላት ውስጥ ተተክሎ ያለው ይህንን ምስቅልቅል ሁኔታ ያለመረዳት ነው። በጭንቅላታቸው ውስጥ የተተከለው መርዝና ሌላውን በንቀት ማየት ያሉበትን ሁኔታ በትክከል ማየት እንዳይችሉ ጋርዷቸዋል። ለምሳሌ በጦር ሜዳ ላይ በነበሩበት ጊዜ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ በስልጣኔ የቀደሙ፣ አማራው ጭራቅ ነው፤ ሰውን ይበላል ብለው ያወሩ እንደነበር ከራሱ ኤርትራዊ፣ ኤርትራ ከሚመላለስ የነሱ ትግል አጋዥ አፍ ሰምቻለው። ይሁንና የደርግን ወታደር ከወያኔ ጋር ድል እያደረጉ ሲመጡ የአማራው ግዛት ውስጥ ይደርሳሉ። ርሃብና ጥማት ስላሰቃየቸው ወደ ቤት ጎራ እያሉ የሚቀመስ ነገር ሲጠይቁ የሚቀርብላቸው እንጀራ በወጥና በእርጎ ነበር። ይህንን ይገነዘባሉ። ኤርትራ ከገቡ በኋላ መሪዎቻቸውን ይጠይቁ የነበረው፣ አማራው ጭራቅ ነው፤ ሰው ይበላል ብላችሁ ነበር የነገራችሁን፤ ሆኖም ግን ርህሩህና ቀና ህዝብ ነው ያጋጠመን እያሉ ነበር የሚነግፘቸው። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ጥቂት ኤሊት ነን የሚሉ የራሳቸውን ስሜትና ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ አንድን ታዳጊ ትውልድ የጥላት መርዝ እንደሚነሰንሱበትና የታሪክ ወንጀል እንደሚሰሩ ነው። ይህ እንደ ዕውነት ሆኖ በጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ እስከ ዕለተ-ሞት ድረስ በመፈራራትና በጥላቻ ይኖራል። የስልጣኔው በር ይዘጋል። የኢትዮጵያችን አንደኛው አስቀያሚ ጎን ይህንን ነው የሚመስለው። ከተራው ህዝብ ሳይሆን ፊደል ከቆጠረውና ዪኒቨርሲቲ ገባሁ ከሚለው የሚነሰነስ የመርዝ ጥላቻ። አቶ ኢስያስ አፈወርቂ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። በጊዜው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን ጋር ሆነን እንታገላለን ያሉ ወደ 400 የሚጠጉ ወጣት ኤርትራውያን በአቶ ኢሳያስ አፈውርቂና በግብረ-አበሮቻቸው እንደታረዱ መታወቅ አለበት። ይህ ጸሀፊ ኤርትራውያን በሙሉ ወንጀለኞች  ናቸው ብሎ አጉል ጥላቻ ለመንዛት አይፈልግም። ብዙ ቀና ጓደኞችም አሉት። ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ የማያስፈልግ የትግል ዘዴ እየታወቀ እንዳንድ ዕውቀት አለን የሚሉ ኤርትራውያን ከውጭ እርማት ለማድረግ ጥረት ያለማድረጋቸው ነው። አንዳንዶቹ ይባስ ብሎ ራሳቸው የዚህ የተሳሳተና መርዝ የትግል ዘዴ ሰለባ መሆናቸውና በውሸት 㗹ዓለም ውስጥ መዋኘታቸው ነው። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ለገሰ አስማሮምን የማያወቀው የለም። ስለ ጋዳ ስርዓት በሰፊው ያጠናና መጽሀፍም የጻፈ ነው። ይህ ፕሮፌሰር ኤርትራ ነጻ ወጣች ከተባለች በኋላ የሚያስተምርበትን ዩኒቨርሲቲ በመተው ከኢሳያስ አፈወርቂ አጋዛዝ ጋር ያበረ ነው። እዚህ የምኖርበት ከተማ መጥቶ ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የሰጠው ትንተና የሚያሳዝንና አንድ ተማርኩ ከሚል አፍ ሊወጣ የማይገባው ውሸት ነው የተናገረው። የማያስፈልገውን ጻፍክ አልባልና፣ የአንድ ምሁር አመለካከት እንደዚህ ከሆነ ካልተማረው ምን ነገር ልንጠብቅ እንችላለን? መማር ማለት መሻሻል፣ በሃሳብ መጽዳትና ለሌላው ብርሃን የሚሆን ነው ብለን ከወሰድን፣ የእነ ፕሮፌሰር ለገሰ አስማሮም ትምህርት ዕውነትን ሳይሆን ውሸትን እንዲጎናጸፉ ነው ያደረጋቸው። ይህ ዐይነቱ የጥላቻ መርዝ ደግሞ በህዝብ ጭንቅላት ውስጥ በመነስነስ የስልጣኔን ብርሃን እንዳያዩ ነው የጋረዳቸው።

       የሰመጥንበት ማጥ በቀላሉ የምንወጣው አይደለም። ያለፈው አልፏል ብንል እንኳ አሁንም በሌላ መልክ እየተከታተለን ነው። ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ለዕውነተኛ ነጻነት ታጋይ ነን ለምንል ኃይሎች ግራ የገባን ኤርትራን በሚመለከት ምን ዐይነት ፖለቲካ እንከተል የሚለው ነው። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የደረስኩበት ድምደማ፣ በማንኛውም መልኩ ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚደረገው መቀራረብ ብዙ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። የኤርትራ መንግስት ድሮም `በነጻነት ትግልም` ዘመን ይሁን  ባለፉት ሃያ አመታት ውስጥ ያስመሰከረው ኢትዮጵያ እንድትበታተን ነው። የኢሳያስ አፈወርቂና ግብረ-አበሮቹ ይህንን ለማንም የማይበጅና ለማንም ግልጽ የማይሆን ፖለቲካ ግባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የማይሸርቡት ተንኮል ይህ ነው አይባልም። ስለሆነም ማንኛውም ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ኢትዮጵያን ከወያኔ መንጋጋ ለማላቀቅ በሚያደርገው ትግል አስቸጋሪ ወጥመድ ወስጥ የገባ ቢሆንም፣ ከእነ ኢሳያስ አፈውርቂ ጋር ሆኜ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጅ ነገር አመጣለሁ ማለት ዘበት ነው። በማንኛውም የፖለቲካ ፍልስፍና የሚደገፍ አይደለም። ኤርትራ ሆኜ፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር ተቀራርቤ ኢትዮጵያን ነጻነት አወጣለሁ የሚለው አስተሳሰብ በፍጹም ሊሰራ የሚችል አይደለም። በታሪኩ ውስጥ ለብዙ መቶ ሺህ ህዝብ ዕልቂት ምክንያት ከሆነ፣ ዛሬም ጭቆናን አስፋፍቶና የራሱን ህዝብ ለስደት ከሚያደርግ መንግስት ጋር ቆሞና ርዳታ አግኝቶ ዕውነተኛ ነጻነት ለኢትዮጵያ ህዝብ አመጣለሁ ማለት በህዝብ ላይ እንደማላገጥ የሚቆጠር ብቻ ሳይሆን ትልቅ የፖለቲካ ወንጀልም እንደመስራት የሚቆጠር ነው። ይህ ጉዳይ በጥብቅ መታሰብ ያለበት ነው። በተረፈ ግን ከኢትዮጵያ ጋር አብረን መኖር እንፈልጋለን፣ የሰለጠነች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ዝግጁ ነን ለሚሉና፣ ከማንኛውም ተንኮል ለጸዱ ኤርትራውያን በሩ ክፍት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ቀናው ምሁር ጠቡ ከኤርትራ ህዝብና በቀና መንፈስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቆሞ ለመታገል ዝግጁ ከሆነው ኤሊት ጋር ሳይሆን፣ ጦርነትንና መተላለቅን ፍልስፍናውና ባህሉ ካደረገው ከኢሳያስ አፈወርቂና ከግብረ-አበሮቹ ጋር ብቻ ነው። ስለሆነም፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግኑኝነት ከኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ባሻገር መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ሊፈታም የሚችለው በፖለቲካና በረዥም ጊዜ የሰላምና የመግባባት ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። ሁለቱም ህዝቦች ለሰላምና ለዕድገት ብለው ቢነሱ ጥሩ ታሪክን ለተከታተዩ ትውልድ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

       የወያኔንና የኦሮሞን ነጻ አውጭ ነኝ ባይን ድርጅቶች ጉዳይ ስንመለከት በተለያየ መልኩ የአንድን ህዝብ መቀራረብና ለጋራ ዓላማ መነሳትን አጥብቆ የሚቃወሙ ናቸው። የሁለቱም ድርጅቶች ችግር የራሳቸውን ታሪክ ከኢትየጵያ ህዝብ ታሪክ ነጥለው በማየትና፣ በነሱ ላይ ይደርስ የነበረውን በደል ብቻ አጉልቶ በማሳየት የታሪክን ሂደት በማጣመም አብዛኛውን ወጣት ማሳሳት ነው። የየራሳቸውን የታሪክ አመጣጥ ባለማገናዘብ፣ በውሸት ቅስቀሳ ላይ በመመርኮዝ፣ ሌላው ወራሪ እነሱ ተወራሪ አድርጎ ማቅረብ የህብረ-ብሄር አመሰራረትን እጅግ በተሳሳተ መልክ ይመለከታሉ። ለምሳሌ ዛሬ የኦሮሞ ኤሊት የኦሮሞ ግዛት ነው ብሎ በባንዲራው ላይ የሳለው ካርታ ከስንት ሚሊዮን ዓመታት ጀምሮ ነበር ኦሮሚያ የምትባል አገር የነበረችው? ኦሮሞዎች ዛሬ የእኔ የግዛት ክልል ነው ብለው በሚጠሩት ከነሱ ቀደም ብለው የዳበሩና በስራ ክፍፍል የላቁ መንግስታት አልነበሩም ወይ?  በታሪክ ውስጥ በማንኛውም አገር የህዝብ እንቅስቃሴ አልነበረም ወይ? በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ህዝብ ወይም ብሄረ-ሰብ ቀድሞ ይኖርበት ከነበረበት ቦታ ተነስቶ ሲሄድና ሌላ አካባቢ ሲኖር፣ በሰፈረበት ቦታ ከሌላው ጋር በመጋባት ልዩ ባህል አይፈጥርም ወይ? ወይም ደግሞ የኗሪውን ብሄረ-ሰብ ባህል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመደምሰስ የሱ ባህል በበላይነት እንዲወጣ አያደርግም ወይ? በጣም በብቸኝነት ከሚኖሩ አናሳ ህዝቦች በስተቀር፣ በማንኛውም አገር የህዝብ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። ስለሆነም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ራሱን ችሎ የሚኖር፣ በአንድ አገዛዝ ስር የተዋቀረ፣ የራሱ ወታደር፣ ቢሮክራሲና በልዩ ልዩ የስራ ክፍፍል የተደራጀ የህብረተሰብ ክፍል በኦሮሚያ ታሪክ ውስጥ የለም። በሌላ አነጋገር፣ ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው ክፍል እንደ ህብረ-ብሄር የተዋቀረ አልነበረም። ኦሮሞዎች ግን በታሪካቸው ከብት አርቢዎች ስለነበሩ ከአንድ ቦታ ፈልሰው በመነሳት በአስራስድስተኛው ክፍለ-ዘመን አብዛኛውን የኢትዮጵያ ግዛት በማዳረስ በንጉስ ደረጃ ተደራጅተው የነበሩ ሌሎች ብሄረ-ሰቦችን በመደምሰስ የተስፋፉ ናቸው። የጋዳም ስርዓት እነሱ እንደሚሉት ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሳይሆን፣ “በመደብ” ላይ የተመሰረተና ሴቶችን ከማንኛውም ተግባርና ከግል ሀብትም ያገለለ የአገዛዝ መዋቅር ነው። ከሞላ ጎደል ይህ ሆኖ ሳለ፣ አፄ ምኒልክ ያደረጉት የግዛት መስፋፋት ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው እንጂ ወረራ አይደለም። የዚያን ጊዜውን ይህን የመሰለውን የታሪክ ሂደት በግንዛቤ ውስጥ ሊገባና ሊመረመር የሚችለው በዚያን ጊዜ የነበረውን ንቃተ-ህሊና ከቁጥር ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው።

       ይሁንና ደግሞ አፄ ምኒልክም ሆኑ እትጌ ጣይቱ በንቃተ-ህሊና፣ በአስተዋይነትና በተራማጅ አስተሳሰብ ዛሬ አለሁ ከሚለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ሆነ የብሄረ-ሰብ መሪ ነኝ ከሚለው ልቀው የሄዱ ናቸው። የዓለም ታሪክና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አወቃቀር ስላልፈቀደ እንጂ የተገለጸላቸው ፍጹም-ንጉስ(Enlightened Absolute Monarchy) ተብለው ለመጠራት የሚችሉ ናቸው።  ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ የዛሬይቱ ኢትየጵያ ምን ዐይነት መልክ እንደሚይዝ አናውቅም። ድርቅ ብሎ ይህ የኔ ክልል ነው፤ የሰው ልጅ ከተፈጠረና ታሪክ መሰራት ከተጀመረ ጀምሮ እኔው ብቻ ነበርኩ በዚህ አካባቢ የምኖረው ማለት በታሪክ ውስጥ በልዩ ልዩ አገሮች የተደረገውን የህዝብ እንቅስቃሴና፣ በመጋባትና በመወላለድ የተፈጠረውን መቀላቀል መዘንጋት ወይም ከቁጥር ውስጥ አለማስገባት ትልቅ የታሪክ ወንጀል እንደመፈጸም ይቆጠራል። ተማርን የሚሉት የኦሮሞ ኤሊቶች የሚሰጡት ትንተና ከህብረተሰብ ሳይንስ ውጭ ነው። በአውሮፓና በአሜሪካ ዪኒቨርሲቲዎች እያስተማሩ- እንዴት እንደሚያስተምሩ አይገባኝም- የኦሮሞ ጥያቄ ሲነሳባቸው ያንገሸግሻቸዋል። ለምሳሌ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያስተምሩ ከተለያዩ ብሄረ-ሰቦች የተውጣጡ ምሁሮችን ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ገለጻ እንዲሰጡ ይጋብዛሉ። ከተጋበዙት ውስጥ ፕሮፌሰር አርአያ ይገኝበታል። ሁሉም በየተራቸው ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሶስዮሎጂ የሚያስተምር ኦሮሞ ፕሮፌሰር ተራ ይደረሰዋል። ንግግሩን የጀመረው በምስጋናና በትህትና ሳይሆን በድንፋታ ነው። ያለው ሀቅ አለ፣ “ትላንትና አማራ ነበር የሚገዛን፣ ዛሬ ደግሞ ትግሬ ነው በቅኝ ግዛትነት የሚገዛን” ብሎ መደንፋት ጀመረ። ተመልከቱት፣ እንደዚህ ዐይነቱ አነጋገር በሶሲዮሎጂ የሚደገፍ አይደለም። የአማራም ሆነ የትግሬ ብሄረ-ሰቦች በጥቅምና በመደብ እንዲሁም በጾታና በዕድሜ የተከፋፈሉ ናቸው። እልም ያለ ገጠር ውስጥ የሚኖረው አማራና ከተማ ውስጥ ከዚህም ከዚያም አካባቢ የመጣው አማራ በንቃተ-ህሊናም ሆነ በህሊና አወቃቀር ይለያያሉ። በገቢም ሆነ በአኗኗር ስልት እንደዚሁ ይለያያሉ። ኦሮሞዎችም እንደዚሁ በአስተሳሰብም ሆነ በአኗኗር ደረጃ ይለያያሉ። በተለይም የኦሮሞ ኤሊት ከተራው የኦሮሞ ብሄረ-ሰብ ጋር ከቋንቋ በስተቀር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ይህንን ሳይረዱ በጥቅሉ አንድን ብሄረ-ሰብ መወንጀልም ሆነ የመጣበትን ብሄረ-ሰብ እወክላለሁ ማለት ስህተት ብቻ ሳይሆን በጣም አደገኛ ነው። ውድ እህቶቼና ወንድሞቼ ተመልከቱት እንግዲህ፣ ምሁር ነኝ የሚለው እንደዚህ ዐይነት ገለጻ ሲሰጥ ከአልተማረው ምን ይጠበቃል? እስካሁን በጥብቅ እንደተከታተልኩት ተማርኩ ከሚለው ፊደል ያልቆጠረው ኢትዮጵያዊ በአርቆ-አስተዋይነት በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ነው። ያም ሆነ ይህ ከአውሮፓ ታሪክ የምንማረው የየህብረ-ብሄሮች አመሰራረት ውጣ ውረድ የበዛበትና፣ ከበደል ነጻ ሊሆን እንደማይችል ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ ህዝብም ሆነ ህብረተሰብ ራሱን ለማወቅና ግንዛቤን ለማግኘት ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅበት የተለያዩ አገሮች ታሪክ ያስተምሩናል። በደልንና ጭቆናን ለመደገፍ ሳይሆን፣ በአገሮች የህብረ-ብሄር ምስረታ ውስጥ በደልና ጭቆና የታሪክ ግዴታዎች መሆናቸውን ብቻ ለማሳየት ነው። ይህንን ሳንገነዘብ የምናደርገው ትግል በሙሉ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠፋፋት ነው የሚያመራን። የምንፈልገውንና የምንመኘውን የመገንጠልም ሆነ አንድነቱን የመመስረቱን ጉዳይ ሳናይ እያረጀንና እየመነመን፣ መጨረሻ ላይ ደግሞ እጅግ ወደሚያሳፍር ቦታ ላይ ወድቀን እንገኛለን። በዚህች አጭር ዕድሜዬ የተመለከትኩት ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ነው። ሰዎች ተምረው፣ የዶክትሬት ዲግሪ ጨብጠው ዘለዓለሙን በጨለማ ዓለም ውስጥ መኖራቸውን ነው። የኑሮ ትርጉሙ ምንድነው?  ለምንድን ነው የምኖረው? ወዴትስ ነው የማመራው? ብሎ የመጠየቅ ጉዳይ፣ በተለይም ተማርኩ በሚለው ጭንቅላት ውስጥ መብሰልሰል ያለበት ጉዳይ ነበር። ስልጣን ለመያዝና የራስን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ተብሎ የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል የማጨለምና የማውደሙ ጉዳይ የተማሩ ሰዎች ተግባር መሆን አልነበረበትም። ከዚህ ስነሳ፣ የኦሮሞ ብሄረ-ሰብ የስልጣኔ ህልሙን ዕውን የሚያደርገው የኦሮሞ ነጻ አውጭ በተለመለት የትግል ስልት አይደለም። የኦሮሞ ብሄረ-ሰብ ፍቅርንና ስልጣኔን ሊቀዳጅ የሚችለው ሳይንሳዊውን የትግል ፈለግ የተከተለ እንደሆን ብቻ ነው።

        የወያኔም ችግር ራሱ ከተፈጠረበት ሁኔታ የመነጨ ነው። የአገራችን ያልተስተካከለ ዕድገት ውጤት ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በትግሬ-ብሄረ-ሰብ ውስጥ የሰፈነ ባህልን ሊያድስ የማይችል የአኗኗር ስልት ከአስተሳሰቡ ጋር በመዋሃዱ ነው። የታሪክን ሂደት በጥልቀትና በሰፊው እንዲመለከት አላስቻለውም። በዚህ ላይ አንዳንዶቹ ከኢኮኖሚና ከህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ አንፃር ከተሻለ አካባቢ የመጡ ስለሆነ ትግላቸውን በአማራና በትግሬ ኤሊት መሀከል የሚካሄድ አድርገው እንዲተረጉሙት ተገደዋል። አፄ ኃይለስላሴ እስከወረዱ ድረስ የአማራ ኤሊት ነበር የሚገዛው፤ አሁን ደግሞ የኛ ተራ ነው ብለው አመቺውን ሁኔታ በመጠቀም ነው ትግላቸውን የጀመሩት። በእነሱ አተረጓጎም፣ በትግሬ ውስጥ ዕድገት ያልታየው የአፄው አገዛዝ በትግሬ ህዝብ ላይ የነበራቸው አመለካከት የቀና ስላልነበረ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው በሌሎች ክፍለ-ሀገሮች ሌላው ህዝብ በዕድገት ሲያሸበርቅ፣ የትግሬ ብሄረ-ሰብ ይህ ዕድል አላጋጠመውም። ዕድገት ምን መሆኑን የማያውቁ ብቻ ናቸው እንደዚህ ብለው የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚተረጉሙት። ሌላው ቢቀር አዲስ አበባ ራሷ እንኳ ኋላ-ቀርነትና ዘመናዊነት፣ ቆሻሻና “ንጽህና” እዚያው በዚያው ጎን ለጎን የሚታዩባት ከተማ ነች። ሀቁ ይህ ከሆነ፣ ታዲያ ሌላው ክፍለ-ሀገር ሲያሸበርቅ ትግሬ ብቻ ነው የተበደለው የሚለው ያላዋቂዎች አነጋገር ከየት ነው የመጣው?

        ህወሃት በአብዛዎቹ አጠራር ደግሞ ወያኔ በአነሳሱ በቁንጽል መልክ የተረጎመውን የማርክሲዝምን-ሌኒንዝምን ርዕዮተ-ዓለም አንግቦ እንደተነሳ የማይካድ ሀቅ ነው። እንደሚታወቀው የማርክሲዝም ርዕዮተ-ዓለም ዓለም-አቀፋዊ ባህርይ ሲኖረው የወዝአደሩን የበላይነት ቢያስቀድምም የመጨረሻ መጨረሻ ግን ማርክስ የሚያምነው በወዝአደሩ አማካይነት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ ይወጣሉ ብሎ ነው። ቲዎሪው ደግሞ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በቴክኖሎጂና በህብረተሰብ አወቃቀር ቀድሞ ከሄደ የካፒታሊስት ህብረተሰብ የፈለቀና በጊዜው የነበረውን የኃይል አስላለፍ ለመለወጥ ታሰቦ የተፈለሰፈ ነው። ማርክስ ይህንን ፍልስፍና ቢያዳብርም የተገለጸለት አስተሳሰብ እንደነበረውና ወያኔ በተረጎመው መልክ ቲዎሪውን እንዳላዳበረ መገንዘብ ይችላል። ወያኔ የፈለቀበትን የህብረተሰብ ክፍልና የማቴሪያል ሁኔታ ስንመለከት ፋብሪካም ሆነ አንድም ወዝ አደር የማይገኝበት ክፍለ-ሀገር ነው። በሌላ አነጋገር ወያኔ የፈለቀበት የህብረተሰብ ክፍል በማቴሪያልም ሆነ በህሊና የተራቆተ ነው። የሚያንጸባርቀውም ሁኔታ ይህንን የማቴሪያልና የህሊና አወቃቀር እንጂ ከካፒታሊስት ህብረተሰብ የፈለቀውን ቲዎሪ አይደለም። ለምሳሌ ወያኔ ዕውነተኛ የማርክሲስት ድርጅት ነኝ ብሎ ቢያምን ኑሮ እ.አ. በ1974 ዓ.ም አብዮቱ ሲፈነዳና እዚህና እዚያ ብዙ ማርከሲስት ነን የሚሉ ድርጅቶች እንደ አሸን ሲፈልቁ በማርክሲዝም የዩኒቨርሳል ቲዎሪ መሰረት ከነዚህ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ጋር ህብረት ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ነበረበት። ይህንን የመተባበር የተቀደሰ ዓላማ ከመከተል ይልቅ የጊዜውን የፖለቲካ ድክመትና ኢትዮጵያ ከብዙ አቅጣጫ የተሰነዘረባትን ጦር በመመልከት ተዳክማለች ብሎ በመገመት የጦር ትግል ለማድረግ ወደ ጫካ ገባ። በድርጅቱ ውስጥ የታቀፉትንም ግለሰቦች ስንመለከት ከአንድ ብሄረ-ሰብ የፈለቁና ራሳቸው በገመቱት መሰረት የዚያን ብሄረሰብ ዓላማ ዕውን እናደርጋለን በማለት ነው ታጥቀው የተነሱት። በታሪክ እንደታየው ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ድርጅቶች የብሄረ-ሰብ ርዕያቸውን ወይም እንደዚህ ዐይነቱን የማርክሲዝም ርዕዮተ-ዓለም አንግበው ሲነሱ የራሳቸውን ውስጣዊ ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ እንጂ የራሳቸውን ብሄረ-ሰብ ነጻ ለማውጣትም ሆነ ተቀብለነዋል ያሉትን ርዕዮተ-ዓለም ተግባራዊ ለማድረግ አይደለም።

       ስለሆነም ስልጣን ከያዙ ከሁለት ዓመት በኋላ ማርክሲዝምን አሽቀንጠረው በመጣል በዓለም አቀፍ ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት የተደነገገላቸውን የገበያ ኢኮኖሚ ነው ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት። በዚህም መሰረት ነው የውጭ ዕርዳታና የፖለቲካ ድጋፍ ሊፈስላቸውና ይሰጣቸው የተጀመረው። በመሆኑም የማርክሲዝምን ርዕይ የሚቃረነውን የነጻ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን ሀብት ለመቆጣጠር የሚችሉበት መንገድ ተከፈተላቸው። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትን ኢንዱስትሪዎችና ትላልቅ የንግድ መደብሮች ግላዊ ሲያደርጉ በተዘዋዋሪ መንገድ እነሱ በመሰረቱት ድርጅት ውስጥ እንዲታቀፉ ወይም ከአገዛዙ ጋር በጥቅም ከተቆላፈፉ ግለሰቦች እጅ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ሀብት ማጋፈፍ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም የዕድገት አቅጣጫ መወሰን ነው የጀመሩት። ከገንዘብ ቅነሳ አንስቶ የውጭውንም ሆነ የውስጡን ገበያ በነጻ ገበያ መሰረት ልቅ ማድረግ አመቺን ሁኔታ የፈጠረው ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን በስልጣን ላይ ቁጥጥ ላሉና ከነሱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩትን ግለሰቦችና ድርጅቶች ነው። በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ግለሰቦችና አንዳንድ ድርጅቶች ሳይሰሩ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ሀብታም ሊሆኑ በቅተዋል። ባጭሩ በወያኔ የሚመራው አገዛዝ ባለፈው ሃያ ዐመታት ተግባራዊ ያደረገው በመንግስት የተደገፈን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ሲሆን፣ ይህ ፖሊሲ ደግሞ ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዳያድግ እንቅፋት የሆነ ነው። ለስልጣኔ ጠንቅ የሆነ፣ የሰፊው ህዝብ አስተሳሰብ እንዲበታተን ያደረገና በራሱም ላይ ዕምነት እንዳይኖረው ያደረገ አደገኛ ጉዞ ነው። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ዛሬ በወያኔና በአፈ-ቀላጤዎቹ የተያዘው ፈሊጥ ወያኔ የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደማይከተልና ተቃዋሚ ኃይሎች ለኒዎ-ሊበራል የገበያ ፖሊሲ እንደቆሙ አድርጎ ነው ዘመቻ የከፈተው። ይህ ዐይነቱ ዘመቻ የሌባ ዐይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ የሚሉት ዐይነት አነጋገር ነው። ያም ተባለ ይህ የወያኔ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትን ፈልፋይ፣ ጥገኝነትን ያጠናከረ፣ በአገሪቱ ውስጥ ሰፋ ያለና የጠነከረ እንዲሁም ሰፊው ህዝብ የሚተማመንበት የማህበራዊና የኢኮኖሚ ተቅዋም መዝርጋት እንዳይቻል ያደረገ ነው። በክልል ፖሊሲ እንዲያምን የተገደደው በተለይም አዲሱ መጤ ኤሊት ይህንን የወያኔን ቅጥ ያጣና አገር አፍራሽ ዓላማ ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡ በመተባበር አንድ ነጻ አገር እንዳይገነባ አግዶታል ማለት ይቻላል። ሰለዚህ ዛሬ ወያኔም ሆነ ግብረ አበሮቹ የኢትዮጵያን ህዝብ ሊያታልሉ የሚችሉበት አንዳችም መፈናፈኛ መንገድ የላቸውም።

        ያም ሆነ ይህ፣ ወያኔ እንደምንም እየተንገዳገደ እዚህ ደርሷል። ራሱ በፈጠራቸው የተወላገዱ ፕሮግራሞችና የገባባቸው ምስቅልቅል ሁኔታዎች ራሱን እንዲጠይቅ በማድረግ ፈንታ አሁንም በእልክ እንዲገፋበት አስገድደውታል። እሱም በተለየ መልክ ብሄረ-ሰቡን ተገን በማድረግና በማስፈራራት የተዳከመውን የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍና የህዝባችንን የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ዘራፊ መንግስትነት(Predatory State)ተለውጧል። ጸረ-ስልጣኔና ፀረ-ሳይንስ በመሆን የአገራችንን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካና የባህል ሁኔታዎች አዘበራርቋል። ወዴት እንደሚያመራም በትክክል ማወቅ ባይቻልም፣ ከሃያ ዐመት በኋላ ብዙም ዘልቆ ሊሄድ እንደማይችል እያረጋገጠ ነው። የማምታት ፖለቲካው ተሟጦ አልቋል። እንዲሁም “የምሁር መሰረቱ” ተሟጦ አልቋል። እስከዛሬም በስልጣን ላይ ሊቆይ የቻለው የሚጋፈጠው ኃይል ስለጠፋ ብቻ ነው።  የኛ ትግልም ከዚህ እልከኛና አልበገርም ባይ አገዛዝ፣ እንዲያም ሲል እጅግ በሚያሳፈር መልክ አገርን በሚቸበችብና፣ አገሪቱን ወደ አስረሽ-ምቺው ሁኔታ በለወጠበት ወቅት እንዴት መላቀቅ ይቻላል ነው። ትግሉ ምን ዐይነት መልክ መያዝ አለበት የሚለው ነው ጭንቅላታችንን ወጥሮ የያዘው። ሰፋ ያለ ምሁራዊ ትግል ማካሄድ ወይስ አሁንም እንደድሮው የትግሉን አድማስ በማጥበብ መደናበር። ከሁለት አንዱን መምረጡ እጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል። በእኔ ዕምነት የትግሉን አድማስ እስካላሰፋነው ድረስና በግልጽ ውጭ ወጥተን እስካልተወያየንና እስካልተከራከርን ድረስ ህዝባችን የሚመኘውን ዕውነተኛውን ስልጣኔ ልናመጣለት እንችልም።

አስቸጋሪው ጉዞአችን-ውሸት ለጊዜው ብታሸንፍም ዕውነት

 ግን መጨረሻ ላይ በድል አድራጊነት ትወጣለች!

                            Pitiful man, who, with the noblest of all tools, with science and art,

                            desires, and obtains nothing higher than the day-labourer with the

                            worst of tools, who, in the kingdom of complete freedom, drags, an

                            enslaved soul around with him. Still more pitiful, however, is the young

                            man of genius, whose natural beautiful stride is led astray by harmful

                           theories and models upon this sad detour, who persuaded to collect

                            ephemeral details for his future vocation, so wretchedly meticulous. His

                            vocational science of patchwork will soon disgust him, desires will

                            awaken in him which it cannot satisfy, his genius will revolt against his

                            destiny. Everything he does appears to him but fragments, he sees no

                            purpose to his work, but purposelessness he cannot bear. The tribulation,

                            triviality in his  professional   business presses him to the ground, because

                            he cannot encounter it with the joyful courage which accompanies only

                            the enlightened understanding, only expected perfection. He feels

                            secluded, torn away from the connectedness of things, since, he has

                            neglected to connect the activity to the grand whole of the world.

                            Jurisprudence disrobes the jurist as soon as the glimmer of a better

                            culture casts its light upon its nakedness, instead of his now striving

                            to become a new creator of law, and to improve deficiencies now

                            discovered out of his own inner wealth. The physician is estranged

                            from his profession as soon as grave errors demonstrate to him the

                             unreliability of his system; the theologian loses respect for his calling

                             as soon as his faith in the infallibility of his system begins to totter.

                             ( Friedrich Schiller- What Is, and to What End Do We Study,

                              Universal History?    Speech delivered to students at Jena University,

                              May, 26-27, 1789)

                 ፕላቶን የሰው ልጅ ሁሉ ትልቁ ችግር የማሰብ ኃይል ችግር ነው።Man’s main problem is the problem of thought or knowledge! ይህ ዐይነቱ ችግር የሰው ልጅ ችግር ቢሆንም-በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤሊቶች አማካይነት በንጹህ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ መመልከት ያስፈልጋል-በተለያዩ አገሮችና ህዝቦች የሚደርሰው ጭቆና ይለያያል። አንዳንዶቹ የሃይማኖትን ልዩነት የግብግብ መነሻ አድርገው ይነሳሉ። ሌሎች ደግሞ ብሄረ-ሰብንና ርዕዮተ-ዓለምን ተገን አድርገው የኔ ይሻላል፣ ስበደል ነበር፣ አሁን ደግሞ የኔ ነው ተራው በሚል የማይሆን ቅራኔ እየተፈጠረ ህዝቦች ለረሃብ፣ ለስደትና ለጦርነት ይዳረጋሉ። በታሪክ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ እንደታየው በተራ ዜጎች መሀከል ቅራኔ የለም። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ችግርን የሚፈጥሩ ምሁራን ነን ወይም ኤሊት ነን ባዮች ናቸው። ኤሊቶች ንጹህ ከሆነው አርቆ-አሳቢነትን ከሚያሰክነው ፕላቶናዊና ሶክራታዊ ፍልስፍናና አስተሳሳብ በመላቀቅ ለራሳቸው ስልጣን መወጣጫ የሚበጃቸውን ርዕዮተ-ዓለም ይፍጥራሉ። ሃይማኖት፣ ርዕዮተ-ዓለሞችና ብሄረ-ሰብ የሚሉት ከሳይንስና ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ ነገሮች ተፈጥረው የሰውን ልጅ እያበጣበጡ ነው።

       የስልጣኔን ታሪክ ስንመረምር፣ የሰው ልጅ ከምንም ተነስቶ ብዙ ነገሮች ፈጥፘል። ከተማዎች ገንብቷል። ካቴድራሎችና መስጊዶች፣ የገበያ አዳራሾችና መናፈሻዎች፣ እንደዛሬው በሰፊው በግሎባላይዜሽን አማካይነት ዕውቀት ቅጥ ባላጣበት ዘመን ነው የተገነቡት። የተለያዩ ህዝቦች ከራሳቸው ክልል በመሻገር በንግድ አማካይነት ባህልን አስፋፍተዋል። በዚያውም አማካይነት የማሰብ አድማሳቸውን አዳብረዋል። አንዱ ከሌላው ተነጥሎ እንደማይኖር በታሪክ ውስጥ አስመስክረዋል። በማሰብ ኃይል ብቻ ዕውነተኛ ታሪክን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ከዕውነተኛ ሃሳብ፣ ከሳይንስና ከጥበብ ውጭ የሚደረጉ ትግሎች ጥፋትን እንጂ ጥቅምን እንደማያመጡ በታሪክ ውስጥ ተረጋግጧል። ታዲያ ለምንድን ነው ራሳችንን የማንጠይቀው? በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የሚኖሩ ህዝቦች ለምን ዕጣቸው ድህነትና መሰደድ ሆነ? የተማርኩ ነኝ ለሚለውና ለማንኛውም ንጹህ ሰው ይህን ዐይነቱን ጥያቄ ለመመለስ ከባድ ባልሆነም ነበር። ይሁንና ግን ሺለር እንዳለው በተሳሳተና በተበጣጠሰ አስተሳሰብ ስለምንመራ፣ ራሳችንን ለመጠየቅ አቅቶን በዚያ መሸምጠጥ እንዳለብን አምርረን ተያይዘናል።

       ስለሆነም በኛ ኢትዮጵያኖች ዘንድ፣ 1ኛ)የፖለቲካ ትግል ከዕውነተኛው ምሁራዊና ዕውቀት ውጭ ተነጥሎ በመታየት፣ ይህ ቅዱስ አስተሳሰብና የብዙ ሚሊዮኖች ዕድል የተንጠለጠለበት የማንም መጨዋቻ ሆኗል፤ ረክሷል። ለምሳሌ በአገራችን የክርስቲያን ባህል ያፈረሰ ቄስ፣ ደብተራና ሴትም ጭምር- የሴቶችን መግባትና አለመግባት የሚያጠያይቅ ቢሆንም- መቅደስ ውስጥ መግባት አይፈቀድላቸውም። መግባት የሚፈቀድላቸው ቄሶችና ዲያቆኖች ሲሆኑ፣ ያላፈረሱ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሳቸውም ከማንኛውም ተንኮልና የእግዚአብሄርን ቃል ከሚፃረር ተግባር የፀዱና በከፍተኛ መንፈሳዊ ተልዕኮ ምዕመናኑን ከእግዚአብሄር ጋር ያገናኛሉ ተብሎ ስለሚታመንበት ነው። ለፖለቲካም እንታገላለን የሚሉ ግለሰቦች በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከማንኛውም ተንኮል የጸዱና ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ለአገርና ለህዝብ ብለው የቆሙ መሆን አለባቸው። አስተዋይ፣ አንድን ነገር ከብዙ አኳያ ማየት የሚችሉና ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት የሚችሉ፣ እንዲሁም ደግሞ የአገሪቱ ህገ-መንግስት ከሚፈቅደው ውጭ መስራትና ውሳኔዎችን መደንገግ የማይችሉ መሆናቸውን የተረዱ መሆን አለባቸው። ቢያንስ ያለፉትን የሃያ ዓመት ትግል ስንመረምር አገዛዙም ሆነ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በራሳቸው ስሜት እየተነሳሱ ነው ፖለቲካን የሚያካሂዱት። ይህ እንደ ባህል የተወሰደ የፖለቲካ ስልት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታረም የሚችል አይመስለኝም። ለታዳጊውና ለመጭው ትውልድ የሚተላለፍ መልዕክት ነው።

       2ኛ) ለህብረተሰብአዊ የፖለቲካ ፕሮጀክት መታገል ማለት በሁሉም አቅጣጫ ሊገለጽ የሚችል ስልጣኔ መታገል ማለት ነው። ዕውነተኛና ሳይንስን የሚያቅፍ ፖለቲካ ወደ ህግ በላይነትና ሲቪል ማህበረሰብ፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚፈራረቅ ልዩ ልዩ ስም የያዙ ፓርቲዎች የሚቀነስ ጉዳይ አይደለም። በሌላ በኩል ግን የህግ የበላይነትም ሆነ የነቃ ሲቪል ማህበረ-ሰብ በሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ የረዥም ጊዜ ክንውኖች ናቸው። በህግ የበላይነትና በፓርቲዎች መፈራረቅ ዙሪያ የሚደረገው ትግልና ከፍተኛ አትኩሮ ለዕውነተኛ ስልጣኔ የሚደረገውን ትግል ይሸፍነዋል። የመጨረሻ መጨረሻም እንዲከስም ያደርገዋል። ዋናው የስልጣኔው ፕሮጀክት ይረሳና ፓርቲዎች ብቻ የሚፈራረቁበትና የሚወነጃጀሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከብዙ አገሮች ልምድ እንደምናየው፣ ከሰላሳና አርባ ዐመታት በኋላም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ለድህነት፣ ለረሃብና ወደ ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ያተኮረ ስደት እጣቸው ይሆናል። ስለዚህ ለስልጣኔ የሚደረገውም ትግል ዕውነተኛ ዲሞክራሲንም የሚያጎናጽፍ መሆን አለበት። ጥቂቶች ብቻ የሚመጻደቁበት መሆን የለበትም። በካፒታሊስት አገሮች በቀጥታ የህዝብ ተሳትፎዎች መኖር አለበት፤ ውሳኔዎች ከጥቂት ፖለቲከኞችና ፓርላሜንታሪያን ብቻ የሚመጣ መሆኑ ቀርቶ፣ በተለይም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚመለከቱ ስራዎች ህዝቡ ውሳኔ መስጠት አለበት እየተባለ ከፍተኛ ትግልና ክርክር ይደረጋል። የውክልና ዲሞክራሲ ብቻ የህዝብን ጥያቄ በትክክል ተግባራዊ አያደርግም እየተባለ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል። ወደኛም ስንመጣ ቀጥታ ህዝባዊ ተሳትፎና ክርክር የሚካሄድበት መድረክ መፈጠር አለበት። የፖለቲካው መድረክ ለጥቂት አውቅን ባዮች መለቀቅ የለበትም።

       3ኛ) የፖለቲካ ትግል በሀቀኛ ክርክርና ውይይት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። የአውሮፓን ረዥሙን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ስንመለከት፣ በክርክር ላይና በጥያቄና በመልስ ላይ የተመረኮዘ ነው። ዕውነተኛ የፖለቲካ ትግል የጥቂት ግለሰቦች ምርኮ በመሆን ሚሊዮን ህዝብ የሚታሽበትና አፉን እንዲዘጋ የሚደረግበት አይደለም። ስለሆነም ዕውነተኛ የፖለቲካ ክርክር ከሳይንስ ውጭ ሊሆን አይገባውም። እንደሌሎችም ይህም ጉዳይ በፖለቲካ ተዋንያኖቻችን ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይደለም። ተረበኞችን፣ ግለሰብ አምላኪዎችን፣ ባንዲራ ለብሰው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ የሚጮሁትን በዕውነተኛ ሳይንሳዊ ክርክር ብቻ ነው መቆጣጠረና፣ ካስፈለገም የትግሉን መድረክ ጥለው እንዲወጡ ማድረግ የሚቻለው። ፖለቲካ በየቡና ቤቱ የሚወራና ወደ ሆያ ሆዬነት የሚቀየር አይደለም። ይህንን መሰረተ-ሃሳብ የማይረዳ ስለ ፖለቲካ ማውራት በፍጹም አይችልም።

       4ኛ) ዕውነተኛ ፖለቲካ፣ ውሸታሙ ከሀቀኛው ተልይቶ የሚታይበት የትግል እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን፣ በረዥም ሂደት የባህል ለውጥም የሚታይበት ነው። የባህል ለውጥ ማምጣት ማለት፣ አንድን ህዝብ ከታሰረበት የውሸት ሰንሰለት አላቆ ዕውነተኛውን ነጻነት እንዲቀዳጅ ማድረግ ማለት ነው። እያንዳንዱ ግለ-ሰብ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ነው። የፖለቲካ ሰዎች በሳይንስ የሚመዘንን የህዝብ ፍላጎት ከህዝብ ጋር ሆነው ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፖለቲካ የራስን አስተሳሰብ መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ በየወቅቱ የራስንም አስተሳሰብ መፈተኛ መሳሪያ ነው። ከላይ የተዘረዘሩት መሰረተ-ሃሳቦች በጭንቅላት ውስጥ ሳይቋጠሩ ስለፖለቲካ ማውራት በፍጹም አይቻልም።

       5ኛ)ያለፉትን የአገራችንን የሃያ ዓመታት ፖለቲካ ታሪክ የተከታተለ ሰው የሚገነዘበው፣ የፖለቲካው ስልት ከላይ እስከታች ሙሉ በሙሉ ፊዩዳላዊ ነው። በማንኛውም ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ የፖለቲካ ፍልስፍናና ቲዎሪ የተደገፈ አይደለም። ትንተና የሚጎድለው፣ ከፍልስፍናና ከቲዎሪ ይልቅ፣ ያልሰሩ ግለሰቦችን ስም አግኖ የሚያቀርብና ተጨባጩን የአገራችንንም ሆነ የዓለም አቀፉን ፖለቲካና የኢኮኖሚ አወቃቀር በሳይንስ መነጽር እንድንመረምር የሚያደርግ አይደለም። በአጠቃላይ ሲታይ፣ የፖለቲካ አየሩ የሰውን ልጅ ምንነት በማይረዱ፣ የህብረተሰብ ህግ ሊገባቸው በማይፈልጉና ከዕውቀት ይልቅ ቁንጹል አቀራረቦችን በሚያስቀድሙ የተወጠረ ነው። ሳይንስና ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን ያላስቀደመ ፖለቲካ መጨረሻ ላይ ወደ ጥፋት ነው የሚያመራን።

       6ኛ) በኢትዮጵያ ምድር ዕውነተኛ ስልጣኔ እንዲመጣና ታሪክ እንዲሰራ ከተፈለገ ለህብረተሰብአችን እታገላለሁ የሚል ሁሉ የነጻ ገበያንና የኒዎ-ሊበራሊዝምን ፍልስፍና አሽቀንጥሮ መጣል አለበት። ታሪክ የተሰራውና አንድ ህብረተሰብ እየተሳሰረ መምጣት የቻለው በመጀመሪያ በንጹህ የነጻ ገበያ አማካይነት አይደለም። በተለይም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ዘንድ የነጻን ገበያ ፍልስፍና በሚመለከት የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። በአንድ አገር ውስጥም ሆነ በአገሮች መሀከል ያለው ግኑኝነት በንግድ አማካይነት የሚገለጽ ቢመስልም፣ በተለይም የብዙ አውሮፓ አገሮችን የህብረተሰብ ግንባታ ለተመለከተ በነቃና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ፓሪስና ብረሰል የመሳሰሉት በማዕከለኛው ክፍለ ዘመን የተገነቡት ውብ ከተማዎች በነገስታትና በአዋቂዎች ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና እንጂ በነጻ ገበያ ፖሊሲ አማካይነት እንዳልሆነ ታሪክ ያረጋግጣል። አንድን ህብረተሰብ ወደ ተራ ሸቀጣ ሸቀጥ ማራገፊያ ነው ልንለውጥ የምንፈልገው ወይም የምንታገለው ካልተባለ በስተቀር ዕውነተኛ ስልጣኔ በመጀመሪያ በፍልስፍና ላይ ብቻ ነው የሚመሰረተው። ይህም ማለት፣ አንድ ህዝብ ራሱን እንዲያውቅና የዕውነተኛ ስልጣኔ ባለቤት እንዲሆን ከተፈለገ አገሩን ሊገነባ የሚችለው በአንድነት ለአንድ ዓላማ ሲነሳ ብቻ ነው። በአውሮፓ ምድር ከአስራሁለተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ውብ ውብ ቤተክርሰቲያናትና ከተማዎች መገንባት ሲጀምሩ በተዘበራረቀና በግለሰቦች ሩጫ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በአንድ መንፈስ ለአንድ ዓላማ ቆርቶ በመነሳቱ ብቻ ነው። ዕውቅ በሆነ በተሃድሶ ላይ በተመሰረተ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚና ሰፋ ያለ የህብረተሰብና የባህል ፖሊሲ ህብረሰተቡን በጋራ በማንቀሳቀስ ግሩም ግሩም ስራዎች ለመስራትና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይቻላል። በአገራችን የፖለቲካ ተዋንያን ዘንድ የተያዘው ፈሊጥ ግን ይህንን በታሪክ የተረጋገጠን የህብረተሰብ ግንባታን ፖሊሲ መከተልና ለሱ መታገል አይደለም። ስለሆነም በተለይም ወጣቱ ትውልድ ታሪክ መስራት ከፈለገ ከቁንጽል አስተሳሰብና ከጊዜያዊ አስተሳሰቦች ባሻገር አልፎ በመሄድ ማንነቱን ማረጋገጥ መቻል አለበት። በፍርሃትና በሃፍረት መዋጥ የለበትም። ይሉኝታን አሸቀንጥሮ ሲጥልና ጥያቄ ማቅረብ ሲጀምር አእምሮው ብሩህ ይሆናል። የዚያን ጊዜ ለታሪክ መስሪያ የሚሆነውን ዕውነተኛ መሰረት መጣል ይችላል።

      7ኛ) አገርን በጋራ ለመገንባትና ለመጭው ትውልድ ውብ ውብ ስራዎችን ጥሎ ለማለፍ ከተፈለገ ዲሲፕሊንና በትዕዛዝ ስራን ለመስራት መዘጋጀት ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። መናናቅ በሰፈነበት አገር፣ የጊዜ ጥቅም በማይታወቅበት እንደኛ ባለ አገር ቅዱስ ዓላማን ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል። በማንኛውም ጭንቅላት ውስጥ መያዝ ያለበት ቁም ነገር ለአንድ አገር ዕድገትና ስልጣኔ ከውስጥ የመነጨ ፍላጎትና ቆራጥነት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ከውስጥ የመነጨ መንፈሳዊ ኃይልን የስልጣኔ መገንቢያ መሳሪያ አድርጎ የተነሳ ተዓምር ሊሰራ ይችላል። በአንፃሩ ግን መንፈሳዊ ኃይሉ የተሟጠጠ ወይም ዕድሉን በውጭ ኃይሎች ላይ ያንጠለጠለ ዕውነተኛ ስልጣኔን ሊቀዳጅ በፍጹም አይችልም። ከዚህ ስንነሳ በአንድ አገር ውስጥ ዕውነተኛ ሀብት ሊፈጠር የሚችለው አንዳንዶች እንደሚሉት በገንዘብ አማካይነት አይደለም። ካልታወቀበት ራሱ ገንዘብ ለጥፋት ምክንያት እንደሚሆን በታሪክ የታወቀ ጉዳይ ነው። ገንዘብና የገንዘብ በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ በፍጥነት መሽከርከር የዳበረ የስራ ክፍፍል ውጤት እንጂ እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊታይ በፍጹም አይችልም። አገር ካለገንዘብ ሊገነባ አይችልም የሚለው አጉል አባባል ብዙዎችን የገንዘብ ቁራኛ አድርጎአቸዋል። አገርን እስከማሸብሸብ እያደረሰ ነው። ብዙዎቻችን በገንዘብ ላይ ያለን አመለካከት እስካልተለወጠና ሁሉንም ነገር በገንዘብ ዙሪያ ለማሽከርከር የምንሞክር ከሆነ ዕውነተኛ ስልጣኔን የማግኘቱ ዕድል የመነመነ ይሆናል። ስለሆነም ብዙዎች የገንዘብን ትርጉም በማጣማም የዕድገትን ዓላማ እያሳሳቱ ነው። ገንዘብ በካፒታሊዝም የዕድገት ሂደት ውስጥ ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እያለ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማያያዝና የንግድ ልውውጥን ለማፋጠን የተፈጠረ ነው። የራሱ የሆነ ሎጂካዊ አመጣጥ አለው። ስለሆነም እንደኛ ባለው የደቀቀ ኢኮኖሚና በካፒታሊዝም ህብረተሰብ ውስጥ የገንዘብ ትርጉም ይለያያሉ። በካፒታሊዝም ህብረተሰብ ውስጥ ገንዘብ ማግኘት የስራ ውጤት ስለሆነ፣ አጠቃቀሙም እንደዚያው ስርዓትን የተከተለ ነው። አንድ ሰው ሀብታም ነኝ ብሎ ገንዘቡን በሆነው ባልሆነው ላይ አያባክንም። ገንዘብን ወደ መዋዕለ-ነዋይነት በመለወጥ የስራ መስክ በመክፈትና ሀብት በማፍራት ኢኮኖሚያዊ ሚናን ይጫወታል።  በተለይም እንደኛ ያለ ደካማና ደሀ አገር ግን የገንዘብ ትርጉም ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይደለም። ህዝባችን በአገዛዙ ደካማነት በመሰርሰርና በውጭ ኃይሎች በመታለል ሀብቱንና ማንነቱን እንዲሸጥ እየተገደደ ነው። ገንዘብ እንደተራ ወረቀት መታየት አለበት። በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል ነው። በተጨባጭ የሚታይ ሀብት ግን በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል አይደለም። ስለዚህም ዕውነተኛ ሀብት በቆንጆ ህንጻዎች፣ በቴክኖሎጂና በተጨማሪም በዕውነተኛ ዕውቀት ብቻ የሚመዘን ነው። የአንድ አገርም ዕድገት ተከታታይነት የሚኖረውና ሊታደስ የሚችለውም ይህ መሰረተ-ሃሳብ ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ብቻ ነው።

       የዛሬው የዓለም አቀፍ ሁኔታ ግልጽ ሁኔታን ፈጥፘል። ባለፉት ሰላሳ ዐመታት በአወቅሁኝ ባይነትና በጉልበት ላይ የተመሰረተ ዓለምን ለማተረማመስና በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ ደሃ አድርጎ ለማቆየት በጥቂት አታላዮች የተበተነው የነጻ ገበያ መፈክር እርቃኑ እየተጋለጠ በመምጣት ላይ ነው። ታሪክን ለመስራትና ስልጣኔን የማያጎናጽፍ መሆኑን እያረጋገጠ ነው። ስለዚህ እንደማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንም ታሪክን በሌላ መልክ ለመስራት አመቺ ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣት ላይ ነው። ይህንን ግልጽ ሁኔታ ጠጋ ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል። በዕድገትና በዕርዳታ ስም መልካቸውን ለውጠው የሚመጡትን ሁሉ ዝም ብሎ አለመከተል ከብዙ አደጋ ሊያድነን ይችላል።

       ዛሬ በአገራችንም ሆነ በውጭ ያለው ችግር ወያኔን የመጣሉና ያለመጣሉ ጉዳይ አይደለም። በኛ መሀከል ያለው የሃሳብ መዘበራረቅና በጠራ መንፈስ ለመታገል ያለመሻት ነው ለትግሉ እንቅፋት የሆነው። ከዚህ እዚህና እዚያ ተቆራርጦ ከሚካሄድ ትግል እስካልተላቀቅንና የመንፈስ አንድነት እስካላገኘን ድረስ ትግሉ የመረረ ይሆናል። የምንመኘውን በፍጹም አናገኝም። እኛም እንደ ብሄረ-ሰብ ታጋዮች እየመነመንና ባለፈው ታሪካችን ብቻ እየተጽናናን እስክናልፍ ድረስ እንኖራለን። ከዚህ አዙሪት ለመላቀቅ እያንዳንዱ ጥረት ማድረግ አለበት። ግለሰብአዊ ነጻነትና ነገሮችን ከሁሉም አንጻር መመርምር ብቻኛና የማያቋርጥ ምርምር ነው ወደ ዕውነተኛው ነጻነት የሚያመራን። ትግሉ ምናልባት የመረረ ሊሆን ይችላል። በየጊዜው ብቅና ጥልቅ የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ይፈጥሩ ይሆናል። የህዝብን ጥያቄዎች እስካልፈቱና የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር በሳይንሳዊ መነጽር መርምረው ፍቱን መፍትሄ ማቅረብ ካልቻሉ እነሱም በበኩላቸው የሚጋለጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዕውነት በአሸናፊነት ትወጣለች።

                                     fekadubekele@gmx.de

Please donate for further philosophical and scientific studies

 ማሳሰቢያ:      የሃሳብ ፍጹማዊነት እንደሌለና ሊኖር እንደማይችል እጅግ

              በጣም ጥሩ በሆነ ይዘት የተዘጋጁ መጽሀፎችን መመልከቱ

              ለትግላችን ያግዛል ብዬ አምናለሁ።

              Feyerabend, Paul, (1989); The Wrong Road of Reason, USA

                                  Orrell, David,        (2010);  Econo Myths: Ten Ways That

                                                                              Economics Gets it Wrong, UK