[gtranslate]

ዘራፊ መንግስት(Predatory State)፣ የዕፅ ጦርነትና(Opium War)

የባህል ውድመት በኢትዮጵያ  ምድር !

                                                                                        ፈቃዱ በቀለ( /)

                                                                                         ታህሳስ 04፣ 2018

መግቢያ

ለ27 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል፣ የአገራችንን ዕድልና ጉዞዋን ሲወስን የነበረውን የህውሃትን አገዛዝ ምንንነት በግልጽ እያየነው ነው። ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ ቡድን እራሱን የነፃ አውጭ ድርጅት ነኝ በማለትና፣ የሌሎችንም ብሄረሰቦች ነፃ አውጭ ነን ባዮች በስሩ በማሰባሰብና የእርስ በርስ ጦርነት በመቀስቀስና በመዝረፍ የአገራችንን ታሪክ፣ ባህሉን፣ ማህበረሰብአዊ ግኑኝነቱንና ስነ-ልቦናውን በመበወዝ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሰርቷል፤ ወይንም የአገራችንን ታሪክ በአዲስ መልክ እንዲጻፍ አድርጓል ማለት ይቻላል።

የህውሃትን አገዛዝ አነሳስ፣ ምንነትና ተግባር በሚመለከት ከተለያዩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋንያንና ጋዜጠኞች የሚቀርቡትን ገለፃዎች በምንመረምርበት ጊዜ በሳይንስ አነጋገር፣ ገለፃ(Descriptive) እየተበላ የሚጠራው አቀራረብ እንጂ፣ ሳይንሳዊ ትንተና እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ገለፃ ነው የሚያሰኘው ማንኛውም ሰው የሚያውቀውን በጽሁፍ ወይም በዜና መልክ ማቅረቡ ሲሆን፣ ውስጣዊ ይዘቱን፣ የርዕዮተ-ዓለም መሰረቱንና ከዓለም አቀፍ የብዝበዛ፣ የፀረ-ዕድገትና የጭቆና አገዛዝ አወቃቀር ተዋረድ( World governance or military industrial complex hierarchy)ጋር የተያያዘ መሆኑን በመመርመር ስለማይጻፍ ነው። የፖለቲካውን ሜዳ እንደዚህ ዐይነቱና ፊዩዳላዊ አቀራረቦች ወጥረው ስለያዙት 27 ዓመት ያህልም ሆነ ከዚያ በፊት በተለይም በአብዮቱ ወቅት የተካሄደውን የፖለቲካ ቲያትር በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በቲዎሪ መልክ በማገናዘብና ተጨባጭ ድርጊቶችን በመተርጎም ለመተንተንና ለማሳመን እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።

እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ የሚከሰቱና የሚያድጉ የፖለቲካ ሁኔታዎች ከሰማይ ዱብ የሚሉ ሳይሆኑ፣ በተለይም በዛሬው ዓለም የዚያው አገር ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አገዛዝና ሁኔታ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ከ1940ዎች መጨረሻ ጀምሮ በአገራችን ምድር የተዋቀረውን የመንግስት መኪናና አገዛዝ፣ የፖለቲካ ግንዛቤ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግኑኝነት፣ እንዲሁም የባህልና የስነ-ልቦና አቀራረጽ በምንመረምርበት ጊዜ በአገራችን የታሪክ ሂደት ውስጥ፣ የመዘበራረቅ ሁኔታና ራስን በራስ ያለማግኘት ጉዳይ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ አወቃቀር፣ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የፀጥታ ጉዳይ ወሳኝ ሚናን እንደተጫወቱ መገንዘብ እንችላለን። በሌላ አነጋገር፣ ከ1940ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ጀምሮ በተለያየ መልክ የሚገለጸው የአገራችን ሁኔታ በውስጣዊ ኃይልና ንቃተ-ህሊና የሚወሰንና የሚታቀድ ሳይሆን በውጭው ዓለም እንደተወሰነና እንደሚወሰን በሳይንስና በቲዎሪ ማረጋገጥ ይቻላል።  ካፒታሊዝም በተንጠባጠበ መልክ ሲገባና በተለይም የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የፍጆታ አጠቃቀምና ባህላዊ ሁኔታ ሲለውጥ በፖለቲካው መስክም ላይ የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ችሏል። እንደዚሁም የሚሊታሪው፣ የጸጥታው፣ የፖሊሲና የሲቪል ቢሮክራሲው፣ እነዚህ ሁሉ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲወርድ ሲዋርድ በመጣና በዳበረ ዕውቀት የታነፁ ሳይሆን አነሰም በዛም የግሎባል ካፒታሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ደግሞ የግዴታ በመንግስት ፖሊሲና የአስራር ሁኔታና የዕድገት ጉዳይ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አላቸው። ስራን በማጓተትና አሻጥር በመስራት፣ የህዝባቸው አለኝታ ከመሆን ይልቅ የውጭ ኃይሎችን ጥቅም በማስጠበቅና ህዝባቸውን በመናቅ አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ  እንደነበር ግልጽ ነው።

ስለሆነም ባለፉት ስልሳ ዓመታት በንቃተ-ህሊና ጉድለት ወይም አዕምሮ አለመብሰል ምክንያት የተነሳ ተማርኩኝ የሚለውና በተለያዩ ጊዜያት በመንግስት መኪና ላይ ቁጥጥ ያሉ አገዛዞች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ፀረ-ዕድገትና ፀረ-ኢትዮጵያ ፖሊሲና ፖለቲካ በመከተላቸው የአስተሳሰብ መዘበራረቅና የእርስ በእርስ ሽኩቻ ተፈጥሯል። ሃሳብን የሚሰበስብና ለጋራ ዓላማ እንድንታገል የሚያደርግ ፍልስፍና ወይም ርዕይ ለመዳበር ባለመቻሉ፣ በተለይም የቢሮክራሲው፣ የተወሰነው የሚሊታሪና የፀጥታው ኃይል የዚህ ወይም የዚያኛው የውጭ የስለላ ድርጅት ሰለባ በመሆን አገራችንን ወደ ጦር አውድማነት ለውጧታል።  ይህ እየተደራረበና እየተወሳሰበ የመጣ ጉዳይ ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት ሁኔታ ዋናው ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። በሌላ ወገን የወጭው ኃይል ሰለባ ያልሆኑ እንደሶብየት ህብረት፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ እንዲሁም ቻይና ጠንካራ ኢኮኖሚና ባህል በመገንባት እራሳቸውን ነፃ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን መፈራትና መከበር ችለዋል። ህዝባቸውም በሄዱበት ሁሉ የሚከበሩ ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔን ዕድገትና የኋላ ኋላ ስልጣን ላይ ወጥቶ የአገራችንን ዕድል 27 ዓመታት ያህል መደንገጉና ታሪክን ማበላሸቱ፣ ወይም ታሪካችን በአዲስ መልክ እንዲጻፍ ማድረጉ የተለያዩ የኢትዮጵያ ኃይሎችም ከውጭው ዓለም በተለይም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ባላቸው የቀረበና የተቆላለፈ ግኑኝነት የተነሳ ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብና እስከዛሬ ድረስ በአገራችን ምድርና በህዝባችን ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን ሰቆቃና መሰደድ የአገዛዙ ድርጊት ብቻ አድርጎ ማቅረብ አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ሳይንስ የአቀራረብና የአተናተን ዘዴ አንፃር ስንመረምረው የተሳሳተ አመለካከትና አቀራረብ ነው። በተጨማሪም የህብረተሰብ ዕድገትን ታሪክ አለማወቅና ከውጭ የሚመጣ የተበላሽ ባህል በስነ-ልቦና ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ አለመረዳት ነው።

ይህንን የአሰራር ስልት ወይም ሳይንሳዊ አቀራረብ መሰረት በማድረግ የወያኔ አገዛዝ ለምን ዘራፊና አገር አውዳሚ፣  እንዲሁም ባህልን ከስካሽና ስነ-ልቦናን አድክሞ አንድ ህዝብ አቅመ-ቢስ እንዲሆን ለማድረግ እንደቻለ ለማሳየት እሞክራለሁ። ለዚህ ደግሞ የወያኔ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ዓለም አቀፋዊ በሚባሉ ተቋማት ተገዶ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወሳኝ ሚናን እንደተጨዋተ ማረጋገጥ ይቻላል።  የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ፣ ከውጭው ዓለም ዕርዳታ ማግኘቱ፣ በዓለም አቀፍ የጦር ስልት ስትራቴጂ ውስጥ በመግባት በአካባቢው ጦርነት በማካሄድና፣ ወደ ውስጥ ደግሞ ግድያን፣ ገረፋን፣ በተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎች ህዝባችንን ማሰቃየትና ወጣቱ እንዲሰደድ ማድረግ፣ ጎሳንና ሃይማኖትን አሳቦ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ማድረግና፣ አገራችንን ዘለዓለማዊ የጦር አውድማ ማድረግ፣ ህዝባችንም የራሱን ታሪክ እንዳይሰራ መሰናክል መፍጠር፣ እነዚህ ሁሉ ከአሜሪካን ኢምፔርያሊዝምና ግብረአበሮቹ የውዝግብና የማተረማመስ፣ የህዝብን ቁጥር ከመቀነስ ስትራቴጂና ፓለቲካ ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው። ስለሆነም ወያኔ ወደ ዘራፊነት የተቀየረውና ሀብትን በከፍተኛ ደረጃ ማውደም የቻለው በግሎባል ካፒታሊዝምና በተቋማቱ በመደገፉ ብቻ ነው። ይህንን የማይቀበል ስለ ዲሞክራሲና ነፃነት እንዲሁም ስለ ሁለ-ገብ ዕድገት በፍጹም ሊያወራ አይችልም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የተከበረች አገር ለመፍጠርም አይችልም።

 

የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊነት ለወያኔ አገዛዝ

ሀብትን መዝረፍ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል !

ወደ ፖሊሲው ተግባራዊነትና አሉታዊ ተጽዕኖ ከመግባቴ በፊት ኒዎ-ሊበራሊዝም ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ጽንሰ-ሃሳቡንና ውጤቱን በሚመለከት በሁላችንም ዘንድ የመረዳት ችግር አለ። አብዛኛዎቻችን የአንድን ጽንሰ-ሃሳብ ወይም ፖሊሲ አፀናነስ፣ ማደግና ወደ ተግባር ተመንዝሮ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዴት ለመያዝ እንደቻለና፣ የጽንሰ-ሃሳቡን ይዘት ለመመርመርና ከህብረተሰብ ዕድገት ጋር ለማገናኘት ገቱ ስለሌን ዝም ብለን እንናገራለን። አንዳንድ የፖለቲካ ታጋይ ነን የሚሉ ድርጅቶች ደግሞ በአገራችን ምድር ምን ዐይነት ፖሊሲ ተግባራዊ እንደተደረገ ሳይመረምሩ የፖለቲካውን ሜዳ በመያዝ የባሰ ውዥንብር ይነዛሉ። አንድን አገር ለመገንባትና እንደማህበረሰብ በፀና መሰረት ላይ ለማቆም ደግሞ የግዴታ የጽንሰ-ሃሳብና የአስተሳሰብ ጥራት መኖር አለበት። አንድ አገር እንደ ህብረተሰብ እንዲገነባ ከተፈለገ ግብዝነትና ፉከራ ወይም ቀረርቶ ቦታ የላቸውም። በመሆኑም የያንዳንዱን የፖለቲካ ድርጅት ወይም አክቲቪስት አቋምና ሀቀኝነት ለማወቅ እንደዚሁ የሃሳብ ጥራት ያስፈልጋል። አንድ አገር ሊገነባና ህዝቡም የተሟላ ነፃነት ማግኘት የሚችለው በሳይንስና በፍልስፍና እየተመራ ንቃተ-ህሊናውን ሲያዳብርና ማንነቱን ሲያውቅ ብቻ ነው።

በመሰረቱ ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ እ.አ በ 1938 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ሲሆን ዋናው መሰረቱም የተጣለው በ1880 ዓ.ም ገደማ ነው። ጽንሰ-ሃሳቡን ባፈለቁ ምሁራን አስተሳሰብና ዕምነት መንግስት በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የገበያውን ተዋንያን ማደናቀፍ የለበትም። ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔና አንድን ህብረተሰብ የሚመለከቱ ጉዳዮች በሙሉ በገበያ ህግ መሰረት መደንገግ አለባቸው። እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ህብረተሰብ አካል የሚታይ ሳይሆን የራሱን ጥቅም ለማሳደግ የሚሯሯጥ ነው። በዚህ ዐይነቱ ግለሰብአዊ ሩጫ የመጨረሻ መጨረሻ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናሉ ይለናል። በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝን የተፈጥሮ ሀብት ቁጥጥር ጉዳይና መሬትንም ጨምሮ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎች ዘንድ በገበያ ህግ የሚደነገግ ወይም እንደ ተሰጠ( as given)ተደርጎ ነው የሚታየው። የቤት ወይም የመኖሪያና እንዲሁም የህክምናና የትምህርት ጉዳይ በገበያ ህግ የሚወሰኑ ናቸው። በኒዎ-ሊበራል አስተሳሰብ አንድ አገር እንደ ገበያ መድረክ ስለሚታይ፣ ባህል፣ ግብረ-ገብነትና ስነ-ምግባር ቦታ የላቸውም። የሚያማምሩ ከተማዎችና ጋርደኖች፣ እንዲሁም የባህል መንደሮች በኒዎ-ሊበራል አስተሳሰብ ውስጥ በግምት ውስጥ የሚገቡ አይደሉም። በመሆኑም ገንዘብ ያለው ብቻ ሁሉን ነገር የሚደነግግበት፣ አንድን ህብረተሰብ እሱ በመሰለው የሚያሽከረክርበት ነው። ደሀና አካለ-ስንኩላት ቦታ የላቸውም። ይህም ማለት የፖሊሲው አውጭዎችና አራማጆች አስተሳሰባቸው ሶሻል ዳርዊኒዝም ወይም አረመኔያዊ አስተሳሰብን(Barbarian Ethos) ያዘለና የፋሺዝም መሰረት ነው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው በተለይም ባለፉት አርባ ዐመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ቫይረስ በመስፋፋት አገሮችን የሚያተራምሰውና ለዘራፊ መንግስታት መሰረት በመሆን አንዱ ሌላውን እየፈራ እንዲኖር የተደረገበት ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው። በዚህ ዐይነት ህብረተሰብ ውስጥ የመንግስት መኪናዎች፣ ማለትም የሚሊታሪው፣ የፀጥታውና የፖሊሱ የጥቂት ሀብታሞችን ጥቅም ማስጠበቂያ በመሆን በህዝብ ላይ ጦርነት እንዲያካሂዱ ለማድረግ በቅተዋል። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆን ህዝብ እንደ እንግዳ ወይንም እንደ አላስፈላጊና ትርፍ(Redundant) ነገር በመታየት በውጭ ኃይሎች በተቀነባበረና በተቀመጠ አገዛዝ ህልውናን እንዲያጣ ለመደረግ በቅቷል ማለት ይቻላል። በማዕከለኛውና በላቲን አሜሪካ አገሮች ያለውን አደገኛ ሁኔታና የህዝብ ፍልሰት መመልከቱ በቂ ምሳሌ ነው።  ከዚህ በመነሳት ነው በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መረዳት የሚቻለው።

የሚያሳዝነው ጉዳይ 27 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ምድር ተግባራዊ በሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ አንዳችም የፖለቲካ ታጋይ ነኝ የሚልም ሆነ የኢኮኖሚ ምሁር አመርቂ ጥናት ለማቅረብ አልቻለም። እንዲያውም በአብዛኛዎቹ ግንዛቤ የወያኔ አገዛዝ እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመንግስት ልማታዊ ፖሊሲና አብዮታዊ ዲሞክራሲ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። በአገራችን ምድር አፍጦ አግጦ ለታየው ቀውስና አገዛዙን እንዲወድቅ ያደረገው ይኸው በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆኑ ብቻ ነው ይሉናል። የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በሚመለከት ከአስር ጊዜ በላይ በሳይንስና በተነፃፃሪ ትንተና(Comparative studies) ለማረጋገጥና ለማሳመን ቢሞከርም ታጋይ ነኝ ባዩና የኢኮኖሚ ተንታኝ ባዩ አሻፈረኝ በማለት አሁንም ድርቅ በማለት „ወያኔ ሲያራምድ የነበረው በመንግስት የተደገፈ ልማታዊ ፖሊሲ ነው“ እያለ ከሳይንስና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ባሻገር ልባችንን ያደርቃል። ይህ ዐይነቱ ችኮነትና ፀረ-ሳይንስ አመለካከት ትርጉሙ ሊገባኝ በፍጹ አይችልም።

ያም ሆነ ይህ በካፒታሊስት አገሮች የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ ዕድገት መመሪያ ተግባራዊ የሆነበት ጊዜ የለም። ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ካፒታሊዝም ስር መስደድና መቆናጠጥ እስከጀመረበት እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት በመንግስት የተደገፈ ፖሊሲ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። በተለያየ ዘመናት ወይም ኤፖኮች እንደ ኃይል አሰላለፍ የተለያዩ የአውሮፓ መንግስታት ጣልቃ-ገብ ፖሊሲዎችን በማካሄድ ለካፒታሊዝም ዕድገት፣ ማበጥና ዓለም አቀፋዊ ባህርይን ለመያዝ ዕምርታን ሰጥተውታል። ይህንን በሚመለከት በሺህ የሚቆጠሩ የኢምፔሪካልና የቲዎሪ ጥናቶች አሉ። የኒዎ-ሊበራሊዝምን ፖሊሲ በሚመለከት አሁን በቅርቡ የወጡ ሁለት መጽሀፎችና የቀድሞው የግሪክ የገንዘብ ሚኒስተር የነበሩት ፕሮፌሰር ፋሮፋኪስ እንደሚያረጋግጡት ኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳልሆነና አገርንም ለመገንባት የሚያመች እንዳይደለ ነው። እንደ ሃይማኖት ከመያዙና ከመሰበኩ በስተቀር ሳይንስ እንዳልሆነ ይነግሩናል። ስለሆነም በአውሮፓው የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው የተለያዩ ዕውቀቶች፣ ማለትም ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የሶስይሎጂና የስነ-ልቦና ዕውቀቶች አንድ ላይ በመጣመራቸውና አንድ ህብረተሰብም እንደ ሁለንታዊ ነገርና እርስ በእርሱ እንደተያያዘ በመታየቱና ግንዛቤ ውስጥ በመግባቱ ነው። አልፎ አልፎ ካፒታሊዝም ፈሩን ሲለቅና ህብረተሰብአዊ ኖርሞች ወደ መላላት ሲያመሩ፣ በተለይም የማህበራዊ ጥያቄዎችና(The Social Question)ባህላዊ ጉዳዮች አትኩሮ እንዲሰጣቸው ከፍተኛና የማያቋርጥ ትግል ይደረግ ነበር። በዚህ መልክ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ምሁራዊ ዕድገት፣ በጥልቀትና በሰፊው ማሰብ፣ እንዲሁም አንድ ህብረተሰብ ተከታታይነት እንዲኖረው የማያቋርጥ ትግል ማድረግ እንደባህል የተወሰዱ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ህብረተሰብ ወደ ገበያነትና መገባያያነት ብቻ ተቀንሶ መታየት እንደሌለበት በተገለጸለቻው የአውሮፓ ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ግንዛቤ ነበር። ይህ ዐይነቱ ግልጽና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ግን በኒዎ-ሊበራሊዝም አይሎ መውጣትና በየተቋማቱ ውስጥ በመሰግሰጉና ፓርቲዎችንም በቁጥጥሩ ስር በማድረጉ ካፒታሊዝም ፈሩን ለቆ በመውጣት ብዙ ህብረተሰቦችን በማተራመስ ላይ ይገኛል። በተለይም የፋይናንስ ካፒታል የበላይነትን መቀዳጀት ሁሉንም የተፈጥሮ ሀብቶችና ሰውንም ጨምሮ ወደ ተራ ሸቀጣ ሸቀጥነት በመለወጡ የኑሮ ትርጉም ሊበላሽ ችሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቶች መስፋፋትና መንግስታት ህግን እየጣሱ የሌላውን አገር ህዝብ ማፈናቀልና መበታተን፣ ሌላውን ደግሞ አመጸኛ እንዲሆን ማድረግ ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ይህ ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲና ውጤቱን መረዳት የሚቻለው።

ለማንኛውም ወያኔ ስልጣን በያዘ በዓመቱ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። በፖሊሲው መሰረትም፣ 1ኛ) የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ እንዲል ማድረግ(Devaluation)፣ 2ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን ወይም የህዝብ ሀብት የሆኑትን ፋብሪካዎችና የንግድ መደብሮችን በሺያጭ ወደ ግል ይዞታ(Privatization) ማዘዋወር፣ 3ኛ) የውጭውን ንግድ ልቅ ወይም ሊበራላይዝ ማድረግ፣ 4ኛ) የመንግስት በጀት ድጎማ በሚደረግላቸው ነግሮች ላይ፣ ምግብ፣ ትምህርትቤትና ጤንነት የመሳሰሉት ላይ በጀቱን መቀነስ፣ 5ኛ) የውስጡን ገበያ በገበያ ህግ  (Demand and Supply)እንዲተዳደር ማድረግ ናቸው የፖሊሲው ይዘቶች። ይህንን ዐይነቱን ፖሊሲ ዴሬጉሌሽን(Deregulation) ብለው ይጠሩታል። በሌላ አነጋገር፣ ኢኮኖሚው እንዳለ ከመንግስት ማነቆ መላቀቅና በገበያ ህግ መሰረት መተዳደር አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ኢኮኖሚው ያድጋል፤ የስራ መስክም ይከፈታል፤ ሰራተኛውም ገቢ ስለሚያገኝ በመግዛት ኃይሉ ለኢኮኖሚው ዕድገት ዕምርታን ይሰጠዋል። በዚያውም የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳለ ይፈነጥዛል ወይም በደስታ ዓለም ውስጥ ይኖራል ይሉናል።

የዚህን ፖሊሲ ውጤት ስንመለከት፣ በተለይም የመንግስት ሀብትን ወደ ግል በማዘዋወሩ ላይ ተጠቃሚ መሆን የቻሉት የወያኔ ሰዎችና ከሱ ጋር በጥቅም የተቆላለፉና ትልቁ ኩባንያው ኢፈርት የሚባለው ነው። ስለሆነም የወያኔ ሰዎች ከባንክ በቀጥታ ብድር በማግኘት ካለምንም ነፃ ውድድር የመንግስትን ሀብት በመቀራመትና ስትራቴጂ የኢኮኖሚ ንዑስ-መስኮችን፣ እንደ እጣን፣ ቡናና ሻይ እንዲሁም ሰሊጥና ኑግን የመሳሰሉትን በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞች ሊሆኑ በቅተዋል። ከዚያም አልፈው የወርቅና ሌሎች በጣም ጠቃሚ የሆኑ ማዕድኖችን በመቆጣጠርና ቆፍሮ እንዲወጣ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ የሀብት ዘረፋ ማድረግ ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪ መሬትን በከተማም ሆነ በገጠር ውስጥ በመቀራመትና ህዝቡን በማፈናቀል የኢትዮጵያን ህዝብ ዕድል በእጃቸው ስር ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን እንደፈለጋቸው ማሽከርከር ችለዋል። ይህ በራሱ ልዩ የሆነና በህይወታቸው ያላለሙትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስታተስ እንዲያገኙና የተንደላቀቀ ኑሮ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። ትላልቅ ቪላ ቤቶችንና መዝናኛ ቦታዎችን በመገንባት ከሌላው የተሻሉ እንደሆኑ ለማሳየት ሞክረዋል። ይሁንና ግን በምሁርም ሆነ በባህል ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ እንዳልቻሉ፣ እንዲያውም እየናጠጡ በመጡ ቁጥር ጭንቅላታቸው እየታወረና የነገሮችን ሂደት ለመገንዘብ ያልቻሉበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ከድርጊታቸው መገንዘብ እንችላለን። በዚህ ዐይነቱ ዐይን ያወጣና ህገ-መንግስቱን፣ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በሚፃረር የሀብት ዝርፊያ ውስጥ እንደነ አላሙዲን የመሳሰሉት በስለላ ድርጅት ውስጥ የታቀፉ ቱጃሮች በመካተት፣ በአንድ በኩል በሀብት ዘረፋነት ሲሰማሩ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፊውን ህዝብ ወደ ድህነትና አቅመ-ቢስነት ገፍትረውታል። በዚያው መጠንም የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማባለግ የባህል ውድመት እንዲፈጠር ለማድረግ በቅተዋል።  በዚህ መልክ ለወያኔ ያደሩ ግለሰቦችን በሀብት ዘረፋ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ አገዛዙ የተወሰነ ደጋፊ ኃይል(Social Base) ለማፍራትና ጭቆናውንና ዘረፋውን ለማስፋፋትና ጥልቀት እንዲያገኝ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮለታል። ይህም ማለት በዚህ ዐይነቱ የዘረፋና የአገር አውዳሚነት ሂደት ውስጥ ከተለያዩ ብሄረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦችም እንደተካተቱበትና፣ ከውጭ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠርና በመተባበር የአገራችን ሀብት እንዲዘረፍና ህዝባችንም እንዲደኸይ ለመደረግ እንደበቁ ማረጋገጥ ይቻላል።

ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተቋም መሰተካከል ዕቅድ(Structural Adjustment Programm) በመባል ሲታወቅ፣ በፕሬዚደንት ሬገንና በወይዘሮ ቴቸር አገዛዝ ዘመን በ1980ዎቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ በታወቀው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ አራማጅ በሚልተን ፍሪድማንና ጓደኞቹ የረቀቀና የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉት የተደነገገ ነው። በአርቃቂዎቹና ኃላፊነትን በሰጡት መሪዎች ዕምነትና ፍላጎት ጠቅላላውን የዓለም ህዝብ በገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ስር በማካተት የአሜሪካንን የበላይነት ማስፈን ነው። ስለሆነም በየአገሮች ውስጥ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍልና አገዛዞች በዚህ ዐይነቱ ዕቅድ ስር በመካተት፣ በአንድ በኩል ወደ ውስጥ የሀብት ሽግሽግና ዘረፋ በማካሄድ ያልተስተካከለ ዕድገት(Unequal Development) ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን፣ ወደ ውጭ ደግሞ ሀብት የሚሸሽበትን ዘዴ ማመቻቸት ነው። ብድርና የተዛባ ንግድ ዋናው የሀብት ዝውውር መሳሪያዎች ናቸው። በዚህ መልክ ፖሊሲው ከጋና እስከናይጄሪያና ዚምባብዌ፣ እንዲሁም በራሺያ ከ1989 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ በማድረግ ለኦሊጋርኪዎች መነሳትና የሀብት መዝረፍ ምክንያት ለመሆን በቅቷል። በእነ ዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕምነት አንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከጠቅላላው ህዝብና ከየአገሩ የማቴሪያል ሁኔታ በመነሳት መነደፍ ያለበት ሳይሆን፣ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ መነሻ በማድረግና በዓለም አቀፍ አገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ በማስገባት ነው መነደፍና መዋቀር ያለበት። ስለሆነም በየአገሩ ውስጥ ያለ ሰፊ ህዝብ እንደትርፍና(Redundant) ጠቃሚ ያልሆነ ሆኖ ነው መታየት ያለብት። ማንኛውም አገር ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ታሪክና ባህል፣ ህብረተሰብአዊ እሴቶችና መተሳሰሮች እንዲሁም ራሱን ወደ ውስጥ የሚመለከትበት ሃይማኖትና ፍልስፍናዊ አመለካከት የለውም። ካለውም ይህንን በሳይንሳዊ ዘዴ መንከባከብና ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የለበትም። በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አራማጆች ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ ያሉና በጭንቅላት ውስጥ የተቀመጡ እሴቶችና ሞራላዊ ነገሮች ለገበያ ኢኮኖሚ እንቅፋት ስለሚሆኑ ከጭንቅላት ውስጥ መደምሰስ አለባቸው። የእያንዳንዱ ግለሰብ ጭንቅላት ምንም ነገር እንዳልተጸፈበት ወረቀት(Tabula rasa) በመሆን የገበያ ኢኮኖሚ መርህን በጭንቅላቱ ውስጥ መትከል አለበት። ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ግለሰብ የገበያ ኢኮኖሚ እያለ መጮህና መዝፈን ይጀምራል። ሰራተኛው ጥቅሙን ለማሳደግ ቀና ደፋ እያለ ሲሰራ፣ አሰሪው ደግሞ ትርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ዘዴዎች ይፈጥራል። ለዚህ ደግሞ ገንዘብ ማግኘት ዋናው ዓላማ ነው።

በዚህ መልክ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደምንመለከተውና እንደምንረዳው የንግድና ሌሎች የአገልግሎት መስኮችን ከማስፋፋትና ዋናው የኢኮኖሚ ዘርፍ ከማድረግ በስተቀር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ ስርዓት ያለው የኢንዱስትሪ ፖለቲካ(Systematic Industrialization) ተግባራዊ እንዲሆን ያገዘ አይደለም። ስለሆነም አድጓል እየተባለ ብዙ የሚወራለት ኢኮኖሚ ስራ ለሚፈልገው ሰፊ ህዝብ የስራ መስክ ለመክፈት የቻለ አይደለም። የአገልግሎት መስኩ ከመንዛዛቱም የተነሳ በአገራችን ምድር የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ከአዳዲስ የፍጆታ ዕቃዎች ጋር በመለማመድ ልዩ ዐይነት የተዛባ ሞራል ሲከሰት፣ በሌላ ወገን ደግሞ ለቅንጦት ዕቃዎች የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ በአገሪቱ የውጭ ንግድ ሚዛን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር ችሏል። የውጭው ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ማደግና ብድሩ መቆለልና በተከታታይ ዕዳ ከፋይ መሆን የዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል።

ከዚህ በመነሳት ነው የወያኔን የሀብት ዘረፋና፣ በሀብት ደልቦ በከፍተኛ ደረጃ በአገራችን ምድር ውስጥ የእስራት ዘመቻ ማካሄድ፣ ህዝብን ማሰርና መግደል፣ እስር ቤት ውስጥ በተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎች ማሰቃየትና አካለ ስንኩል እንዲሆኑ ማድረግን መረዳት የሚቻለው። የሀብት ዘረፋን ጥልቀትና ስፋት ለመስጠት ደግሞ የግዴታ የመጨቆኛ መሳሪያውንና የስለላ ድርጅቱን በረቀቀ መልከ ማዘጋጀት አለበት። ለዚህ ደግሞ ጠቅላላው ሰለጠንኩኝ የሚለው፣ የህግ የበላይነትና የሰብአዊ መብት መከበርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ነው ጥረቴና ትግሌ የሚለው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገር በስተጀርባው እንደቆመና ማንኛውንም የጭቆናና የስለላ መሳሪያ ያቀርብለት እንደነበር ግልጽ ነው። 27 ዓመታት ያህል የምዕራቡ ዓለም በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የወያኔ አገዛዝ የሚያደርገውን የሀብት ዘረፋና ጭቆና እንዲሁም ግድያ የሚያውቀው ነገር የለም ብሎ መናገር በህዝባችንና በታሪኩ ላይ መሳለቅና መቀለድ ነው። ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉና በኮንግረስ አማካይነት እርምጃ እዲወሰድ ቅስቀሳ ማድረግና መለማመጥ የዚህ ዐይነቱ ዐይን ያወጣ ዘረፋና አገር አውዳሚ፣ እንዲሁም ህዝብ ገዳይ ድርጊት ተባባሪ እንደመሆን ነው የሚቆጠረው።

የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ለምድን ነው እንደዚህ ዐይነቱን ዘራፊና ህዝብን ጨቋኝና ገዳይ አገዛዝ አቅፈው ደግፈው ግፋበት የሚሉት?  ለምንድ ነው በዕርዳታ ስም በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያፈሱለት? ነገሩ ቀላል ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ያልተገለጸለትና የታሪክ ግንዛቤ የሌለው አገዛዝ የዕውነተኛ ስልጣኔ ጠንቅ በመሆኑ ብቻ ነው። በተጨማሪም በራሱ የሚተማመን ኢንደስትሪየስ የሆነ የከበርቴ መደብ ብቅ እንዳይልና ህዝብ በራሱ ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ለማድረግ ነው። ስለሆነም አንድን ህዝብ በዕርዳታ ስም አቅመ-ቢስ ማድረግና ሞራሉን አዳክሞ ለዘለዓለም ተገዢ ማድረግ ዋናው የኢምፔሪያሊስት አገሮች ስትራቴጂ ነው። በዚህ መልክ በአፍሪካ ምድር ውስጥ እንደ ጃፓንና ቻይና፣ እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ የመሳሰሉ በራሳቸው የሚተማመኑ አገሮች እንዳይዳብሩና ተቀናቃኝ እንዳይሆኑ ጨቋኝና ዘራፊ አገዛዞችን መደገፍና አንድ ህዝብ እንዲበወዝ ማድረግ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አካሂድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠበቃ ቆሚያለሁ ለሚለውና እዚህና እዚያ ባንዲራ ለሚያውለበልበው፣ እንዲሁም በየሚዲያው እየተጋበዘ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጥና ለራሳቸውም ጋዜጠኛ ነን ባዮችና የሚዲያ ሰዎች ግልጽ መሆን ነበረበት፡፡ እንደማየው ከሆነ በከፍተኛ ደረጃ የጭንቅላት መደንዘዝ ተስፋፍቷል። በምድር ላይ የሚካሄዱ ነገሮችን የማየት፣ የመመርመርና የመተንተን ችግር አለ። የግሪክ ፈላስፎች እንደሚሉት ጭንቅላት ማየት የማይችል ከሆነ ዐይንም ማየት አይችልም እንደሚሉት፣ በተለይም ምሁር ነኝ የሚለው የሚሰጠውን ትንተና የሚባል ነገርና ገለፃ ስመለከትና ስሰማ የምረዳው ነገር የቱን ያህል የምሁር ክፍተት እንዳለ ነው የምገነዘበው። ነገሩ በግራና በቀኝ አመለካከት በሚሉት የአወናባጆችና የፋሺሽቶች ስም ማጥፊያ ዘዴ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በሳይንስ፣ በቲዎሪና በፍልስፍና መነፅር ብቻ ነው። ችግሩም እዚህ ላይ ነው እንጂ የግራ ናፍቆት ጉዳይ አይደለም። በመሰረቱ የሰው ልጅ የግራና የቀኝ አስተሳሰብ ሊኖረው በፍጹም አይችልም፣ ወይም ደግሞ የግራ ወይም የቀኝ አስተሳሰብ የሚባል ነገር የለም። ሊኖር የሚችለው ሳይንሳዊ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት ነው። ሊኖር የሚችለው ልዩነት በራሺናሊዝም ላይ የተመሰረተ ፍልፍናዊና ሰብአዊ አመለካከት ወይም ደግሞ አርቆ-አሳቢነት የጎደለው፣ አንድን ነገር ነጣጥሎ የሚያይና በነገሮች መሀከል መተሳሰር የሚሉት ነገር የለም ብሎ በሚያምን  መሀከል ብቻ ነው። ባጭሩ በዓለምም ሆነ በአገራችን የሚካሄደው ትግልና ያለው ልዩነት፣ በአንድ በኩል ሰብአዊነትን በሚሰብኩና በሚያራምዱ፣ እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ እኩልነት(Economic and political justice) በሚታገሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባልተገለጸላቸውና ኢ-ሰብአዊነትን በሚያራምዱና በስልላ መረብ ውስጥ በመግባት ህዝባዊ ኃይል እንዲበታተን በማድረግ የድህነትና የመፈናቀል ዘመኑ እንዲራዘም ለማድረግ በሚጥሩ ሰይጣናዊ ኃይሎች መሀከል ነው። ከዚህ ስንነሳ ለአንድ ህዝብና ለአንድ አገር ችግር መመርመሪያው ዘዴ ሳይንሳዊ ቲዎሪ እንጂ የግራና የቀኝ አመለካከት አይደለም። ዋናው ቁም ነገር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በተለያየ የታሪክ ኤፖክ የሚከሰቱ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነቶች፣ ማህበራዊ ችግሮችና የርስ በርስ ግጭቶችን በሳይንስ የመመርመሪያ ዘዴ በመመርመር አነሰም በዛም መፍትሄ ለመስጠትና ታሪካዊ አስተዋፅዖ ለማድረግ ብቻ ነው። በአንድ አገር የሚኖር ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የሚቆጠር የሚሆነውን የማይሆነውን ነገር በሚያወሩ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በመወናበድ ፈሩን እንዳይለቅ መጣር እንጂ ማስፈራሪያ ነገር ጣል እያደረጉ መጠራጠርን  በማስፋፋት የባሰውን በህዝብ ዘንድ አለመተማመን እንዲኖር ማድረግ አይደለም የአንድ ምሁር ሚናና ታሪካዊ ተልዕኮ።

ከዚህ በመነሳት በአገራችን ምድር ብቻ ሳይሆን በብዙ የአፍሪካ አገሮችና፣ የማዕከለኛውና የላቲን አሜሪካ አገሮች ያለውን የተዘበራረቀና የጭቆና እንዲሁም የዘረፋ ሁኔታ ስንመለከት በቅርጽ ይለያዩ እንጂ በይዘት አንድ ናቸው። በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተዋቀሩት አገዛዞች በሙሉና፣ የመንግስት የጭቆና መኪናዎች ጭምር ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ማንኛውም አገር ቢሆን ከአገሩ ሁኔታ በመነሳትና የአገሩን ህዝብ ፍላጎት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መንግስታዊ መኪናን ያዋቀረበትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አርቅቆ ተግባራዊ ያደረገበት ጊዜ የለም። በመሆኑም ነው  በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ከውስጥ አለመረጋጋት የሚኖረው፤ ህዝብ የሚጨቆነውና ሌላው ደግሞ የሚሰደደው። ይህንን ነው የምዕራቡ ዓለም የሚያራምደውና በራሳቸው የሚተማመኑ አገዛዞች ካሉ ደግሞ በኩዴታ መልክ እንዲገለበጡ የሚያደርገው። ነገሩ ግልጽ ነው። ይህች ዓለም በነጩ የኦሊጋርኪ መደብ መዳፍ ስር መዳሽቅ አለባት፤ በዓለም ላይ ያሉ የጥሬ-ሀብቶች በሙሉ በምዕራቡ ዓለም ቁጥጥር ስር መዋል ያለባቸው ናቸው። እያንዳንዱ አገርና መንግስት ራሳቸው በመሰላቸው መንገድ ኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን መቀየስ የለባቸውም። በመጀመሪያ ደረጃ የህዝባቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሙላት የለባቸውም። ከዚያም በኋላ ቀሰ በቀስ ጠቅላላውን ኢኮኖሚያቸውን በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት በመገንባት ጠንካራ ህብረተሰብ መመስረት የለባቸውም።  ጉዳዩ በዚህ መልክ ነው መታየት ያለበት። በዚህ መልክ ማየት የማይችል ወይንም የማይፈልግ ስለነፃነትና ዲሞክራሲ፣ እንዲሁም ስለኢትዮጵያ አንድነት ማውራት በፍጹም አይችልም።

 

የዕፅ ጦርነትና(Opium War) ጠንቁ በአገራችን ምድር !

የዕፅ ጦርነት(Opium War) በመባል የታወቀው ጦርነት የተካሄደው በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ሲሆን መነሾውም እስከዚያ ጊዜ ድረስ በጊዜው የነበረው የቻይና መንግስት ገበያውን ለምዕራቡ ዓለም፣ በተለም ለእንግሊዝ ክፍት ባለማድረጉ ነበር። ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የውጭ ንግድ አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱ ሲታወቅ እንግሊዝና ሆላንድ በተለይም የጥሬ-ሀብት ያላቸውን አገሮች ማሰስ ይጀምራሉ። እንደቻይና የመሳሰሉት አገሮች እንደ ሀር፣ ከፖርሴላን የተሰሩ ልዩ ልዩ የቤት ዕቃዎችንና ሻይ ወደ አውሮፓ በመላክና ወደ ውስጥ ደግሞ ገበያቸውን በመቆጣጠራቸው ወይም ክፍት ባለማድረጋቸው የእንግሊዝንና የተቀሩትን የምዕራብ አውሮፓ የውጭ ንግድ ሚዛን ማዛባት ይችላሉ። ምክንያቱም እንግሊዝም ሆነ ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከቻይና የሚመጡ ዕቃዎችን ስለሚፈልጉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ቻይና በራሴ ምርት ብቻ መወሰንና ፍላጎቴንም ማሟላት እችላለሁ በማለቷና በሯን በመዝጋቷ  በጊዜው እንደገንዘብ የሚያገለግለው ከብር የተሰራ ገንዘብ ወደ ቻይና በመፍሰስ የእንግሊዝንና የተቀሩትን አገሮች የንግድ ሚዛን ያዛባል። በዚህ የተናደደችው እንግሊዝ የነበራት አማራጭ በአካባቢው አገር ኦፒየምን በማምረትና በተለያየ መልክ በማስገባት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ መፍጠር ነው። ስለሆነም በተለይም በንግድና በጉምሩክ መስሪያ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ቻይናዎች ኦፒየምን በማጨስ ጥገኛ በመሆናቸው ይህ ጉዳይ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን መፍጠር ቻለ። በዚህ መልክ ቻይና ገበያዋን እንድትከፍት ተገደደች። ይህ ዐይነኡ የኦፒየም ጦርነት በሙዚየም መልክ ቻይና ውስጥ ይታያል።

ወደ አገራችን ስንመጣ ጦርነቱ በዚህ መልክ የተካሄደ ሳይሆን ዘራፊ መንግስትን ስልጣን ላይ በማስቀመጥ በዚያ አማካይነት በተለይም ወጣቱን የዕፅ ሰለባ በማድረግ ለስራ፣ ለፈጠራና ለህብረተሰብ ዕድገት ያለውን ውስጣዊ ፍላጎት ማኮላሸት ነው። በዚህም መሰረት ቀስ በቀስ ህብረተሰቡን በማደንዘዝ አገርን በተለያዩ የኢኮኖሚ መሳሪያዎች መቆጣጠርና የባሰ ማሽመድመድ ነው። ተጨባጩን ሁኔታ ስንመለከት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በጣም ፈጣን በሆነ መልክ ዕፅ ማጨስና ጥገኛ መሆን፣ ጨአት መቃምና የጨአት መቃሚያ ቤቶች መስፋፋት፣ ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ሴት ልጆች በየመንገዱ እየቆሙ ሰውነታቸውን እንዲሸጡና በተለያዩ የአባለ-ዘር በሽታዎች እንዲለከፉ ማድረግ፣ የአስረሽ ምችው ቦታዎች መስፋፋትና የአልክሆል ሱሰኛ መሆን፣ የተለያዩ ሃይማኖት የሚመስሉ ነገሮች በመግባት ህብረተሰቡን ግራ ማጋባት… ወዘተ.፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተስፋፉትና ህበረተሰብአዊ እሴቶች ሊበጣጠሱ የቻሉት በአገዛዙና በውጭ ኃይሎች በተቀነባበረ ጦርነት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ነን የሚሉና የአረብ ነጋዴዎች የተከፈተላቸውን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም በአገራችን ብዙም የማይታወቅ በወንዶች መሀከል የሚካሄድ የወሲብ ግኑኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ ህብረተሰቡ እንዳለ ሊበወዝ ችሏል። በዚህም ምክንያት የደርግ አገዛዝ ስልጣን ላይ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ በኤይድስ ቫይረስ የተለከፈው የህብረተሰብ ቁጥር ከአንድ በመቶ በታች ሲሆን፣ ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ በኤይድስ ቫይረስ የተለከፈው ህዝብ ቁጥር ወደ 5% በመቶና ወደ 7% አድጓል። ይህ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው በብዛት ያልተስፋፉ በሽታዎች፣ እንደ ልብ በሽታ፣ ስኳርና የጉበት በሽታዎች በመስፋፋት ህብረተሰብአዊ ቀውስ ሊፈጠር ችሏል። በተለይም ቆሻሻ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በመግባታቸውና በየቦታው በመጠላቸውና ስለሚጣሉ ገንዝብ ለማግኘት የሚፈልገው ወጣት ለጤንነት አደገኛ የሆኑ የማዕድን ውጤቶችን በሚፈልግበት ጊዜ ወዲያውኑ ለአደጋ ይጋለጣል። እንደምንከታተለው ከሆነ በተለይም ወጣቱ በዚህም ሆነ በሌላ ምክንያት ካለ ዕድሜው በልብ በሽታ እንዲጠቃ ተደርጓል። ከዚህም ባሻገር የወጣቶችን ኦርጋን መሸጥ እየተለመደ መጥቷል።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ህብረተሰብ በዚህ መልክ ሲወጠር የማሰብ ኃይሉ እንዳለ ይደመሰሳል። ዕውነትን ከውሸት ለመለየት የማይችልበት ሁኔታ ስለሚፈጠር አገሩን እንዳለ ለወጭ ኃይሎች ክፍት በማድረግ ራሱንና አገሩን እንዳለ ይሸጣል። ዶላርና ኦይሮ እንደብርቅ በሚታዩብት አገር ደግሞ አንዳንዱ ልጆቹንም እስከመሸጥ ይደርሳል። ዋናው ነገር ሆድ መሙላቱ ላይ ስለሆነ  አብዛኛው ህዝብ በዚህ መልክ ህብረተሰብአዊ እሴት እንደሚበጣጠስ አይረዳም። በተለይም የነቃ ምሁራዊ ኃይል በሌለበትና ሁሉም በየፊናው በሚሯሯጥበት አገር ያልተማረው ሰፊ ህዝብ የሚያደርገውን ነገር በቅጡ ለማገናዘብ አይችልም። የሀፍረት ገበና የሚባለው ነገር ከጭንቅላቱ ተሟጦ ስለሚጠፋ ማንኛውንም እሴትንና ባህልን የሚጥሱ ነገሮች ሁሉ ከማድረግ አይቆጠብም። በአጭሩ ጭንቅላቱ ስለሚደነዝዝ ሞትንም እንደቁም ነገር ስለማይወስድ ዛሬ የተደረገውን ነገር ወዲያውኑ ይረሳል። ጭቆናንና መሰደድን፣ ሴት ልጆችን ወደ አረብ አገር በመላክ ገንዘብ ማግኘት እንደተራ ነገር ስለሚታዩ አንድ ሰው ማድረግ ባለበትና  በሌለበት መሀከል ያለውን ልዩነት ስለማይገነዘብ አንድ ህብረተሰብ መጨፈሪያና ቀስ በቀስ ደግሞ ወደ ጦር አውድማነት ሲለወጥ ዝም ብሎ ይመለከታል። በዚህ መልክ የአንድ ህብረተሰብ የሞራል ኮምፓስ የሚሉት ነገር እንዳለ ይደመሰሳል። ህብረተሰቡ ወዴት እንደሚጓዝ፣ ከየት እንደመጣና ለምንስ በዚህች ዓለም ላይ እንደሚኖርና ታሪካዊ ሚናውንም ስለማይረዳ ጮሌዎችና አገር አከረባባቾች እየመጡ ሲበውዙት ዝም ብሎ ይመለከታል። በራሱ የሚተማመን ዜጋ የማይሆንና በአምላክ ምስል የተፈጠረ እንዳይደለ ይደረጋል።

ከዚህ ስንነሳ በግልጽ ከሚታየው ጦርነት ይልቅ የአገራችንን ህልውና የበጣጠሰውና ለማስተካከልም የሚችግረው ይህ ዐይነቱ በረቀቀ መልክ የሚካሄድ የኢምፔርያሊስቶች የዕፅ ጦርነትና፣ የወያኔና አንዳንድ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያደሩ ኃይሎች መንገድ አመቻችነት ነው። ይህንን ጦርነት ለመዋጋትና ህበረተሰቡን በአዲስ አስተሳሰብ አንጾ ጠንካራ አገር ለመገንባት የግዴታ ጠንካራና በራሱ የሚተማመን መንግስት ያስፈልጋል። ከዚህም ባሻገር ለህብረተሰቡ አለኝታ የሚሆን የተገለጸለትና ነገሮችን በግልጽ የሚናገር ደፋርና የታሪክን አደራ ለመቀበል የተዘጋጀ ምሁራዊ ኃይል እጅግ አስፈላጊ ነው። በህብረተሰብ የግንባታ ታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው በአንድ አገር ውስጥ በልዩ ልዩ ዕውቀት የታነፀና የዳበረ ምሁር ብቻ ነው መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው። አብዛኛውን ጊዜ ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉ ኃይሎች በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚካሄዱ ነገሮች ስለማይታያቸውና፣ በተለይም በአሁኑ ዘመን በውጭ ኃይሎች ስለሚታለሉ ወይም በነሱ መረብ ውስጥ ስለሚገቡ አንድን ህብረተሰብ ወደ ውስጥ ጠጋ ብሎ የመመልከት ኃይል የላቸውም። በመሆኑም በሶስዮሎጂ፣ በፍልስፍና፣ በህሊና ሳይንስና በተፈጥሮ ሳይንስ የሰለጠኑ ምሁራን ተከታታይ ጥናት በማድረግ ህብረተሰቡ በቀናና ዕድገት አጋዥ በሆነ መስመር ላይ እንዲጓዝ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው።

መደምደሚያ !

ህዝባችን ከ27 ዓመት የጭቆናና የአፈና አገዛዝ ተላቆ ቢያንስ የነፃነት አየርን መተንፈስ ከጀመረ ወደ ሰባት ወር ይሆነዋል። የማቴያል ሁኔታዎች ባይሟሉለትም በዚህ መልክ የረካ ይመስላል። በሌላው ወገን ግን የዶ/ር አቢይ አገዛዝ አስቸጋሪና በቀላሉ የማይወጣው ሁኔታ ውስጥ እንዳለ እናውቃለን። እስካሁን ድረስ አገዛዙ የተቻለውን ነገር ቢያደርግም በሌላ በኩል የቱን ያህል የሃሳብ ጥራት እንዳለና ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮችን አመጣጥ በሚመለከት በቂ ግንዛቤ ይኑር አይኑር የሚታወቅ ጉዳይ የለም። እንደሚታወቀው ለአንድ ነገር መፍትሄ መስጠት የሚቻለው የመነሾው ምክንያት ሲታወቅ ብቻ ነው። ይህም ማለት ለጭቆናዊ አገዛዝ፣ ለኢኮኖሚው ድቀትና፣ አብዛኛው ህዝብ በድህነት ዓለምና በቆሻሻ ቦታዎች ውስጥ መኖር፣ የሀብት ዘረፋና በተለይም ወጣቱ ትውልድ የልዩ ልዩ ዕፆች ሰለባ መሆንና ራሱን እንዲዘነጋ ማድረግ፣ የእሴት መበጣጠስና በራስ አለመተማመን… ወዘተ. ለእነዚህ ነገሮች ምክንያታቸው መታወቅ አለባቸው። ምንክንያቱ ሲታወቅ ብቻ ነው ተቀራራቢ የሆነ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው። በተለይም የውጭ ኃይሎችን ሚናና የተራድዖ ድርጅቶችን ተግባርና አስተዋፅዖ መመርመርና አስፈላጊና አላስፈላጊ መሆናቸውን በጥናት መልክ መቅረብ ያለባቸው ጉዳይ ነው። ከዚህ ሁሉ የሚያስቸግረው ከአሜሪካ ጋር ያለው የጠበቀ ግኑኝነትና በስለላ ድርጅቱ አማካይነት የሚያካሂድብን ጦርነት በሚገባ መጠናት ያለበት ጉዳይ ነው። ይህንን በሚመለከት ሁላችንም የመሸነፍ መንፈስ አለብን። ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስንወዳደር ራሱን የጣለ እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር የለም ማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ  ምሁሩ ሳይንሳዊ ጥናት ለማድረግ ፍላጎት ስለሌለውና በሚጽፍበትም ጊዜ ከገለጻ(Desciptive) የአመለካከት ዘዴ ለመላቀቅ አለመቻሉና በትዝታ ዓለም ውስጥ መገኘቱ ነው። በተጨማሪም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተኮተኮተውና ከሞት የተረፈው አንዳንድ የሚሊታሪና የሲቪል ቢሮክራሲ፣ እንዲሁም ከሲአይኤ ጋር በማበር በአብዮቱ ላይ በመዝመት የቀይና የነጭ ሽብር ተዋናይ የነበረው፣ እነዚህ ሁሉ በመደመር ስም አሁንም ስለሚያወናብዱና በየዋሁና ዕውቀት በሌለው ወጣትና ጋዜጠኛ እንደትልቅ ሰዎች ሆነው በመታየታቸው የፖለቲካው መድረክ ወደ ሴሌብሪቲነትና መቀለጃነት ተለውጧል ማለት ይቻላል። ፖለቲካው የሰለጠነና ግልጽነት ያለውና ጭንቅላትንም ከማደስ ይልቅ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ባላቸው ኃይሎች እየተከበበ በመምጣት ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚደረገውን ትግል እያጨለመው ነው ማለት ይቻላል። ይህ ማለት ግን የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ለመቃወም ሳይሆን ያለውን ውስብስብነትና የአወናባጆችን መግበስበስ ለማሳየት ብቻ ነው።

ወደድንም ጠላንም አንድ አገር ሊነሳ፣ ሊያድግና ጠንካራ አገር ሊሆን የሚችለው በሳይንሳዊ አስተሳሰብና በፍልስና ሲመራ ብቻ ነው።  የመንፈስ ተሃድሶና ዕውነተኛ ዘመናዊነትም ዕውን ሊሆኑ የሚችሉት በሳይንሳዊ መሳሪያ ብቻ ነው። ከግሪክ ስልጣኔ እስከ ሬናሳንስና ሪፎርሜሽን፣ እንዲሁም ኢንላይተንሜንት ድረስ የተደረገውን ትግል ስንመለከት በአንድ በኩል ሳይንስና በሳይንስ ላይ የተመረኮዘን ስልጣኔን በሚሹና ለዚህ ጠበቃ በሆኑ፣ በሌላ ወገን ደግሞ አንድ ህዝብ ጭንቅላቱን እንዳይከፍትና የስልጣኔን ብርሃን እንዳያይ በሚፈልጉ ኋላ-ቀር ኃይሎች መሀከል ነው። በአገራችንም ያለው ትግል በዚህ መልክ መካሄድ ያለበት ሲሆን፣ መንፈሳዊ ተሃድሶን ለማምጣትና ንቃተ-ህሊናን ለማሳደግ የሚያስችለውን መንገድ የማግኘት ችግር እንዳለ በግልጽ ይታያል። በዓለም ባንክ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችና የአመለካከት ጥራት የሌላቸው በመግባት ውዥንብር በመንዛት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። ያም ተባለ ይህ ያለን የቤት ስራ በቶሎ ቶሎ ሩጫና ልታይ ልታይ በማለት የሚቀረፍ ሳይሆን ረጅም ጉዞ የሚያስኬድና ዕምነትንና የመንፈስ ጽናትን የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም ወደ ውስጥ ኃይልን መሰብሰብና ለሰላም፣ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና እንዲሁም ለህዝባዊ ብልጽግና የሚደረገው ትግል የሰከነና የተቀነባበረ መሆን አለበት። የሃሳብ አንድነት(Unity of Thought)ሲፈጠርና የሃሳብ ጥራት ሲኖር ብቻ ነው አንድን ህዝብ ነፃ ማውጣት የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ !!

 

                                                                           fekadubekele@gmx.de