[gtranslate]

ፖለቲከኞች ነን ባዮች በፖለቲካ ስም የሚሰሩት ታላቅ የታሪክ ወንጀል-ክፍል አራት!!

 

                                                                                       ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                         መስከረም 29 2020

 

ድንቁርና ከግንዛቤ ድክመት የተነሳ ሊከሰት የሚችል ነው ብሎ መገመት ድንቁርናን ዝቅ አድርጎ መመልከት ነው። ድንቁርና ከዚህ በላይ የሆነ ነው። በጣም ተንቀሳቃሽ፣ ቀናተኛ፣ ስግብግብና ካለአግባብ ለእኔ ይገባኛል በማለት ሀብት የሚያግበሰብስ፣ ዓለምን በጠባብ መነፅር የሚመለከት፣ ካለአግባብ አንድ ድርጊት እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሚሰጥ፣ ሌሎችን የሚያገል ነው። በየጊዜው ሃሳቡን የሚለዋውጥ፣ ይሁንና በምንም ዐይነት ተሳሳትኩ ብሎ የማያምን ነው። የወደፊቱን ሁኔታ በሚያሽበርቅ ቀለም የሚስል፤  ቀለሙ  ግን ተለዋዋጭ ነው።  ድንቁርና የታሪክ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። በዓለም ላይ የተስፋፋ በመሆኑም ማንም ሰው ከዚህ ዐይነቱ በሽታ ሊያመልጥ የሚችል አይደለም። በማንኛውም የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ከሱ ጋር የማይገናኝ የለም። ስለሆነም ሁሉም በእሱ ፊት እኩል ነው። ከኃያላኖች በላይ ኃያል የሆነ ነው። ዛሬ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ርዕዮተ-ዓለሞች ጋር ሲነፀፃር አምባገነኖች ተዝናንተውና ተረጋግተው እንዲገዙ የሚያደርግ ይኸው ድንቁርና የሚባለው ነገር ነው።፡ በዓለም ላይ ትላልቅ ጦርነቶች እንዲቀሰቀሱ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ሁሉም ሳይወድ በግድ ወገናዊ በመሆን ጦርነት እንዲሟሟቅና እንዲስፋፋ ያደርጋል። በዛሬው ወቅት ከመደብ ትግልና በትውልዶች መሀከል ከሚደረግ ግጭት ወይም ጠብ ይልቅ በድንቁርና ላይ የሚደረገው ዘመቻ ከፍተኛውን ቦታ መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው። ከምንጊዜውም የበለጠ ድንቁርናን መዋጋት የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የድንቁርና ኃያልነት ከሚለው ከፈረንሳዩ ፈላስፋና የሶስዮሎጂ ምሁር አንድሬ ግሉክስማን „The Power of Ignorance“ መጽሀፍ የተወሰደ ጥቅስ።

 

 መግቢያ

ፖለቲካ ብለን ከጠራነው የአገራችን ፖለቲካ ሁላችንንም ግራ እያጋባን ነው። በፖለቲካው ውስጥ ቁጥራቸው የማይታወቁ የዚህን ወይም የዚያኛውን ብሄረሰብ መብት እናስከብራለን፣ ወይም ደግሞ የአገራችን የወደፊት አቅጣጫ ያስፈራቸው የተለያዩ ድርጅቶችና፣ በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝና „የብልጽግና ፓርቲ“ የሚባለው የፖለቲካውን መድረክ በማጣበባቸው ሁሉም ድርጅቶችና ስልጣንን የጨበጠው አገዛዝ በምን ርዕይ ወይም ፍልስፍና እንደሚመሩ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚህ ውስጥ በጣም ግራ የሚያጋባው የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ነው። ራሱ ግራ ተጋብቶ በአብዛኛዎቻችን ላይ ከፍተኛ የመንፈስ አለመረጋጋትና ውዝንብር በመንዛት ለመከፋፈል በቅቷል። ዶ/ር አቢይ በሚያሳዩት ፈገግታና አሳሳች ፖለቲካ የተማረከው ቁጥሩ አነሰ የማይባል ኃይል ዛሬ በአገራችን ምድር የሚካሄደውን፣ በተለይም በአማራው ብሄረሰብና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረውን ጭፍጨፋና ማፈናቀል ከሳቸው ቁጥጥርና ግንዛቤ ውጭ እንደሆነ ለማሳመን ይሞክራል። በተለይም እንደኔ የመሳሰሉ የፖለቲካ ተንታኞችና የተወሰነ አቋምና የአሰራር ስልት ያላቸው የሚጠይቁት ጥያቄ፣ ለመሆኑ መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? ተግባሩስ ምንድነው? ማንንስ ነው የሚወክለው? ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ወይስ አንድን ብሄረሰብ? ተግባሩስ ገብቶታል ወይ? በሚያራምደው እርስ በርሱ የተምታታ ፖለቲካ በእርግጥስ የኦሮሞ ብሴረሰብን መብት ሊያስጠብቅ ይችላል ወይ? የኦሮሞ ብሄረሰብስ ፍላጎት ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት በምን ይለያል? እንደዚህ ዐይነቱ በፖለቲካ ቲዎሪም ሆነ በፖለቲካ ፍልስፍና የማይደገፍ አካሄድ የመጨረሻ መጨረሻ ያልታቀደ ህብረተሰብአዊ ግጭት (Social conflict) አይፈጥርም ወይ? እንደዚህ ዐይነቱ ወደ ውስጥ ያልተረጋጋ ሁኔታ የሚፈጥር ፖለቲካ አገራችንና ህዝባችንን አደጋ ውስጥ አይጥሏቸውም ወይ? ዶ/ር አቢይም ሆነ በአከባቢያቸው የተሰባሰቡት ኃይሎች በሙሉና፣ የሚሊታሪውና የፀጥታ ኃይሉም ጭምር የዓለም ፖለቲካና የዓለምን ፖለቲካ እንደፈለግን ማሽከርከር እንችላለን፣ በፈለግነው ጊዜም በአንድ አገር ውስጥ አጋጣሚ ሁኔታዎችን ተጠቅመን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ማድረግ እንችላለን የሚሉትን የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችንና አጋሮቻቸውን ሚና መረዳት ይችላሉ ወይ?  የአንድ አገርስ መሪና መንግስት እንደዚህ ዐይነቱን አደገኛ ፖለቲካ የመከተል መብት አለው ወይ? ህገ-መንግስቱስ ይፈቅድለታል ወይ? እያልን ነው ብዙ ጥያቄዎችን የምናነሳው።

ዶ/ር አቢይ ስልጣንን ሲረከቡ አብረው የተረከቧቸው እጅግ አስቸጋሪ የቤት ስራዎች እንዳሉ ሆነው፣ እሳቸውና በእሳቸው አካባቢ የተሰባሰቡት በሙሉና፣ ለስሙ የአማራውን ብሄረሰብም ሆነ የሌሎችን ብሄረሰቦች መብት እናስከብራለን በማለት የስልጣን ተካፋይ የነበሩትና ያሉት በሙሉ ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር ህውሃት በበላይነት አገሪቱን ሲመራ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያን ለመበታተን ያልሰራው ወንጀል እንደሌለ ነው። በማንኛውም አገር ታሪክ ውስጥ በማይታወቅ መልኩ አንድ የረጀም ጊዜ ታሪክና ባህል ያላት አገር ዛሬ በምናያት መልኩ የተበወዘችውና አቅጣጫው የጠፋበት አገር በፍጹም የለም። ከሁለት ዐመት ተኩል ጀምሮ የለውጥ ኃይሎች እያልን የምናሞግሳቸው ግለሰቦች በሙሉና-ለምን የለውጥ ኃይሎች እየተባሉ እንደሚጠሩ ግራ የሚያጋባ ነው– ድርጅቶች ከወያኔ ጋር አብረው ሲያቦኩና፣ በማውቅም ሆነ ባለማወቅ በጥፋት ፖለቲካው የተሳተፉና፣ አንዳንዶችም ግፋበት እያሉ ነገሩን ያሟሟቁ ናቸው።  የአንድሬ ግሉክስማንን ጥቅስ ለማስታወስ ያህል፣ ህውሃትም ሆነ የሱ አጫፋሪዎችና የዛሬው አገዛዝ ለምን እንደዚህ ዐይነቱን አገርን የጥፋትና የመጠፋፋት ፖለቲካ ለመከተል ተገደዱ? ደንቆሮ ስለሆኑ ወይስ ሆን ብለው? ሆን ብለው እንደዚህ ዐይነት ታሪክን የሚያወድምና ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ ግራ የሚያጋባ ፖለቲካ በመከተላቸው ምን ዐይነት ጥቅም አገኙ? ቁጥራቸው በእርግጥ የማይታወቁ ሰዎችን ሲገዱልና ሲያሰቃዩ ምንስ ዐይነት ደስታ ተጎናጸፉ? አምሳሎቻቸውን፣ እህቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን በመግደልና በማሰቃየት ያገኙት ትርፍ አለ ወይ? ማንንስ ለማናደድ ነው እንደዚህ ዐይነቱን የጥፋትና የዕልቂት ፖለቲካ የተከተሉት? የእንደዚህ ዐይነቱ የጥፋት ፖለቲካ የመጨረሻው ዓላማስ ምንድነው? ፖለቲካ የሚባለውን ነገር በዚህ መልክ በመረዳታቸው? ወይስ ከመጀመሪያውኑ ጭንቅላታቸው ለጥፋት በመዋቀሩና፣ትምህርት በሚሉት ነገር መቃናት ወይም መታደስ የማይችል በመሆኑ?  ከእነዚህ ጥያቄዎች በመነሳት አሁንም የአንድሬ ግሉክስማንን ጥቅስ መሰረት በማድረግ አርባ ዐመት ያህል በፖለቲካ ስም የተጓዝንበትን መንገድ ለመቃኘት እሞክራለሁ።

                                    የትግል ዋና ዓላማው ምንድነው?

በፖለቲካ ትግል ውስጥ ተሳተፍንም አልተሳተፍንም በአጠቃላይ ሲታይ ህይወት እራሱ ትግል ነው። ይሁንና ግን አብዛኛዎቻችን አብዛኛውን ዕድሜያችንን በደመ-ነፍስ እየተመራን ነው የምናሳልፈው። በጣም ዘግይተን ካልሆነ በስተቀር ይህንን ነው የምፈልገው፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ነው ቀን ተሌት መስራት ያለብኝ ብለን የህይወትን ትርጉም በመረዳት ደፋ ቀና የምንለው በጣም ጥቂቶች ነን። ከራሴ ጀምሮ ስንቶቻችን ሰው መሆናችንን ጠይቀን እንደሆን፣ የሰው ልጅስ ተግባሩ ምን እንደሆነና፣ ለምንስ ደፋ ቀና እንደምንል የምንጠይቅ ምናልባት በጣም ጥቂቶቻችን ሳንሆን አንቀርም። በተጨማሪም ከሌሎች ህይወት ካላቸው ነገሮች ጋር ስንወዳደር ምን ዐይነት ባህርይስ እንዳለን ለመጠየቅ የምንችል በጣም ጥቂቶቻችን ነን። በሌላ አነጋገር፣ የማሰብ ኃይል እንዳለንና በማሰብ ኃይላችን መደረግ ካለበት ከሌለበት፣ መጥፎውን ከጥሩ ነገር በመለየት በአርቆ አሳቢነት የምንመራ በጣም ጥቂቶች ነን።  በእርግጥ ማለት ይቻላል ሰው መሆናችንን የምንገነዘብና የታሪክ ተልዕኮ እንዳለን በመረዳት አንድ ጥሩ ነገር ሳልሰራ ከዚህች ዓለም ላይ በሞት ለመለየት አልፈልግም የምንል በጣም በጣም ጥቂቶች ነን። እኛ ብቻ ሳንሆን ምናልባትም ከ90% በላይ የሚሆነው የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ የሚመራና ለአንድ የተወሰነ ዓላማ የሚታገል አይደለም። አብዛኛዎቻችን በሁኔታዎች የምንመራና፣ ጥቂት ሰዎች በፈጠሩት የምንደሰትና፣ እንደዚሁም በጥቂት ሰዎች እየተመራን ነው አብዛኛውን ህይወታችንን የምናሳልፈው። ይሁንና ግን ሁላችንም ብንሆን በህይወታችን ዘመን ከሀዝንና ከጎስቋላ ኑሮ ይልቅ ደስተኛነትንና የተሳካ ኑሮ ቢኖረን ደስ ይለናል። ስንወጣም ስንገባም ማንም ባይገላምጠንና ህይወታችን በሙሉ ሰላም የሰፈነበትና የተወሰነ ዓላማን ተከትሎ ቢመራ ደስተኞች ነን።

ይሁንና ግን ኑሮአችን የተቃና እንዲሆን፣ ምናልባትም የምንመኘውን ነገር ለማግኘት የምንችለው እኛው በምናደርገው መፍጨርጨር ብቻ አይደለም የሚወሰነው። በመጀመሪያ ደረጃ የወላጆቻችን ሁኔታ፣ የአስተዳደጋችንና የአካባቢያችን ሁኔታ፣ የተማርንበት ትምህርት ቤትና በጠቅላላው በተወለድንበት አገር ያለው የፖለቲካ ሁኔታና የሰላም መኖር  በህይወታችን ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ካልሰፈነ፣ የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጠው ኃይል የሚሰራውን የማያውቅ ከሆነ፣ የአገር ወዳድ ስሜት ከሌለውና ለውጭ ኃይሎች አጎብዳች በመሆን የአገርን ሀብት የሚያወድምና ባህልን የሚያበላሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የአብዛኛዎቻችን ህይወት ይበላሻል። ያጋጠመውና ብልጣብልጥ የሆነው በጣም ጥቂት ኃይል ደግሞ የተበላሸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጠቃሚ በመሆን የተሻለ ኑሮ የሚኖርበት ሁኔታ አለ። የ27 ዓመቱ የወያኔ አገዛዝና ኢኮኖሚ ፖሊሲው ይህንን ነው የሚያረጋግጡት። በጣም ጥቂቱ ተጠቃሚ የሆነበትና፣ አብዛኛው ደግሞ ወደ ድህነት ዓለም የተገፈተረበትን ሁኔታ እንመለከታለን።  ከዚህ ውስጥ ጥቂቱ አገሩን ጥሎ በመውጣት ሌላ አገር የተሻለ ዕድል  ለማግኘት ደፋ ቀና ሲል እናያለን። ጥቂት የማይባለውም ወገናችን የስቃይ ኑሮ እንደሚኖርና፣ የተወሰነው ደግሞ የሚፈልገውን ወይም የሚመኘውን ነገር ሳያገኝ ህይወቱ እንዳለፈ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

ኑሮን ለማሸነፍ ሲባል በግለሰብ ደረጃ የሚካሄደውን ትግል ትተን በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚደረገውን ትግል ስንመለከት እንደዚሁ በአማዛኝ ጎኑ ርዕይ የሌለውና ዓላማ ቢስ ነው ማለት ይቻላል። ቀድሞም ሆነ ዛሬ ያሉት ድርጅቶችና ፓርቲዎች በምን ዐይነት ርዕይ እንደሚመሩና ለምንስ ዐይነት ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ እንደሚታገሉ ግልጽ አይደለም። ፍልስፍናቸው፣ በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲያቸው ካልታወቀ እንታገልለታለን ለሚሉት የህብረተሰብ አካልና ወይም ደግሞ ብሄረሰብ የቀን ተቀን ችግሩን ሊፈቱለት አይችሉም። ፍልስፍናና ርዕየ-አልባ የሆነ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የአንድን ህዝብ ፍላጎት ማዕከላዊ ቦታ የማይሰጥ የትግል ፈሊጥ የመጨረሻ መጨረሻ ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ነው የሚፈጠረው።

የአንዳንድ አገሮችን ወይም አገዛዞችን የእልቂት ፖለቲካ ወደ ጎን ትተን፣ የአገራችንን ፖለቲካ ጠጋ ብለን ስንመለከትና ስንመረምር በፖለቲካ ስም ፖለቲካ ውስጥ ሰተት ብለው የገቡ፣ ወይም የጦር ትግል ያካሄዱ ትግላቸውን የጀመሩት ካላንዳች ዐይነት ርዕይ ወይም ፍልስፍና ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የርዕይ መኖር ወይም በአንዳች ፍልስፍና መመራት በምንም ዐይነት ትግልን ውስብስብ ስለማያደርግ ነው፤ ሰውን አያጨራርስም፤ የአንድን አገር ታሪክ እንዳለ እንዲካድ አያደርግም፤ በተቻለ መጠን ለትግል የሚከፈለው መስዋዕትነት በጣም ዝቅተኛ እንዲሆን ይደረጋል። ርዕይ የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ ከጥሩ ነገር ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን አንድን ግለሰብ ወይም ድርጅት የተቃራኒውን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ምንም ነገር የለም። ይህም ማለት፣ በርዕይ ወይም በአንዳች ፍልስፍና የሚመራ ሰው ወይም ድርጅት የሚፈልገው ግብ ጋ ለመድረስ የግዴታ ሰውን መግደል የለበትም፤ ወይም የጥፋት ፖለቲካ አያካሄድም። በራሱ ውስጣዊ ፍላጎት ስለማይመራና ከሱ ባሻገርም የሌላ ሰው ህይወት እንዳለ የሚገነዘብ በመሆኑ ስራው ሁሉ በዕውቀትና በሀቀኝነት ላይ የተመረኮዘ ይሆናል ማለት ነው።

አብዛኛውን ጊዜ አብዛኛዎቻችን ከአርባ ዐመት ጀምሮ በአገራችን ምድር የደረሰውን የጥፋት ወይም ርዕየ-ቢስ ትግል ለማያያዝ የምንሞክረው የራሳችንን ፍልስፍና በመከተላችን ሳይሆን ሶሻሊዝም የሚባለውን ከውጭ የመጣ ርዕዮተ-ዓለምን በመቀበላችን ነው የሚል ነው። ስንቶቻችን የማርክስና የኢንግልስን ስራዎች እንዳነበብንና፣ በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም ከተካሄደው የእርስ በርስ መተላለቅ ጋር እንዳነፃፀርነው የሚታወቅ ነገር የለም። የማርክስና የኤንግልስ ስራዎችም በብዙ ሺሆች የአውሮፓውያንና የአሜሪካን ምሁራኖች ተተርጉመዋል፤ ተተንትነዋል። የማርክስንና የኤንግልስን ኦሪጂናል ስራዎችም ሆነ በተለያዩ ምሁራን የተተነተኑትንና የተተረጎሙትን መጽሀፎችና መጽሄቶች በምናነብበት ጊዜ አንዳችም ቦታ ላይ በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ወይም ስልጣን ላይ ለመውጣት ከተፈለገ የግዴታ በከፍተኛ ደረጃ የሰው ልጅ ህይወት ማለቅ አለበት የሚል የለም። ለምሳሌ የማርክስን ስራዎች፣ ሶስቱን ቅጾች ዳስ ካፒታልን ላነበበ፣ ስርፕለስ ቫልዩ የሚባለውን ለተመለከተ፣ እጅግ ግሩም የሆነውን መሰረታዊ ስራውን (Ground Work) ላገላበጠ፣ የጀርመን አይዲዮሎጂንና የጂውሽ ጥያቄ የሚባሉትን መጽሀፎች ላነበበ፣ የፍሪድሪሽ ኢንገልስን አንቲ-ዱህሪንግ(Anti Dühring) …ወዘተ… ወዘተ. ለተመለከተ ወይም ላነበበ፣ በእነዚህ መጽሀፎች ውስጥ በሙሉ ስለ እርስ በርስ መተላለቅ አስፈላጊነት ወይም በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ መገዳደል ያስፈልጋል ወይም ደም ካልፈሰሰ አብዮቱ አይሰምርም ወይም ባሸናፊነት መውጣት አይቻልም የሚል አንዳችም ቦታ ላይ አልተጻፈም። በተጨማሪም ማርክስና ኤንግልስ የሰው ልጅ ታሪክ የመደብ ትግል ነው ብለው ሲጽፉ ይህ ማለት ግን እየተቧቀሱና እየተጨራረሱ የሚኖሩ፣ አንደኛው ሌላውን ካላጠፋ የፈለገው ዓላማ ወይም ሶሻሊዝም ላይ ሊደርስ አይችልም ያሉበት ቦታ የለም። የመደብ ትግል የሚባለው ነገር የግዴታ ከአመፅ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ፣ ርዕዮተ-ዓለማዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ…ወዘተ. መልኮችን የሚይዝና፣ የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጠው ኃይል እንደንቃተ-ህሊና ደረጃው የበላይነቱን ላለማጣት ሲል የተለያዩ ዘዴዎችን በመፈለግ ህብረተሰብአዊ ተቀባይነቱን ለማረጋገጥ ይችላል ማለታቸው ነው። ይህ ዐይነቱን ሁኔታ የቀን ተቀን የምንመለከተው ጉዳይ ነው። በተለይም አንድ ዐይነት ስርዓት ተቀባይነት ካገኘ-ለምሳሌ የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም፣ እንደ ርዕዮተ-ዓለም ወይም እንደ ሃይማኖት ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። በሌላ ወገን ደግሞ እንደ አማራጭ የሚቀርቡ ስርዓቶች ወይም ኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ተፈጥሮአዊ አይደሉም፣ ተፈጥሮአዊ ይኸው ተቀባይነተን ያገኘው ስርዓት ነው በማለት በሰፊው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እንዳያገኝ ከፍተኛ ትግል ይደረጋል። ትግሉ በጦርነት ሳይሆን በሃሳብና በክርክር ብቻ ነው። ይሁንና ግን በተለይም በአውሮፓ የህብረተሰብና የካፒታሊዝም የትግል ታሪክ ውስጥ የኢኮኖሚና የፖለቲካ በላይነትን የጨበጠው ኃይል ዝም ብሎ በጉልበት ወይም በብልጣብልጥነት የበላይነቱን ይዞ የሚቆይ ሳይሆን ስርዓቱ እንዳይናጋ ወደድርድር እንደሚመመጣና በውይይት ብቻም የሚቀርቡትን ጥያቄዎች እንደሚፈታ በተለይም ያለፈው ሃምሳ ዐመታት የካፒታሊዝም ዕድገትና ስረዓተ-ማህበሩ ያረጋግጣሉ።

ይህንን ትተን ወደ ማርክስና ኤንግልስ ስራዎች እንደገና ስንመጣ፣ ስራዎቻቸው በሙሉ ምሁራዊና ከእነሱ አተረጓገምና የአሰራር ስልት አንፃር ሳይንሳዊ ናቸው። በሌላ ወገን ግን የማርክስና የኤንግልስ ስራዎች በሙሉ አንድ ህብረተሰብ እንዴት እንደሚገነባ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች እንዴት እንደሚፈልቁና እንደሚዳብሩ፣ ከተማዎችና መንደሮች እንዴት እንደሚገነቡ በቀጥታ አይናገሩም። የከበርቴው ኢኮኖሚስቶችም ሆነ ሌሎች ምሁሮች አንድ ህዝብ ሁለ-ገብ በሆነ መልክ እንዴት መዋቀር እንዳለበት የተሻለ አማራጭ አያቀርቡም። በተለይም በኔዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት ሁሉንም ነገር የገበያ ኢኮኖሚ ይፈታዋል በማለት ነው ነገሩን አደባብሰው ያልፋል።  አንድ አገር በዝግታና ስርዓት ባለው መንገድና ከጠቅላላው ህዝብ ፍላጎት አንፃር መገንባት እንዳለበትና አስፈላጊም እንደሆነ በፍጹም አይቀበሉም።ለማንኛውም ማርክስና ኤንግልስ አንድ ህብረተሰብ እንደማህበረሰብ ለመኖር ከፈለገ የግዴታ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አስፈላጊ እንደሆኑና፣ ይህም በካፒታሊዝም ስርዓተ-ማህበር ውስጥ ተግባራዊ እንደሆኑ በግልጽ ተንትነዋል። ከዚህም በላይ ዕውቀት አስፈላጊና አንድ ህብረተሰብም ንቃተ-ህሊናው መዳበር እንዳለበት፣ በዚህ አማካይነት ብቻ፣ በእነሱ አጠራር የምርት ኃይሎች ማደግና በየጊዜው መሻሻል እንደሚችሉ በደንብ ጽፈዋል። የማርክስና ኤንግልስ ስራዎች በጊዜው የነበረውን በካፒታሊዝም ሎጂክ የሚንቀሳቀሰውን ስርዓት ትችታዊ በሆነ መልክ(Critical analysis) የተመለከተና የተነተነ እንጂ ስለሾሊስት ህብረተሰብ አወቃቀር የሚያትት አይደለም። ይሁንና በካፒታሊዝም ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ሊዳብሩና ሊስፋፉ፣ እንዲሁም ዓለምን ሊያዳርሱ የበቁት ቀደም ብሎ በሚገኘው ስርዓት ውስጥ በመፍለቃቸው ነው። ይህም ማለት ከካፒታሊዝም በፊት የነበረው ስርዓት ሙሉ በሙሉ  ዕድገትን የሚቀናቀን ነው ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። ከተማዎችና መንደሮች ጥበባዊ በሆነ መልክ የተገነቡት፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎችና የንግድ እንቅስቃሴ የዳበሩትና የተስፋፉት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረቶች በሙሉ ቀደም ብሎ ባለውና በፊዩዳሊዝም ስርዓት ውስጥ ነው የፈለቁት። ለማርክስና ኤንግልስ ይህ ነገር ግልጽ ነው።

ከዚህ ትንተና ወይም አቀራረብ ስንነሳ በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የተካሄደውን መጨራረስ በማርክሲዝምና በሶሻሊዝም ስም የምናሳብበት ምክንያት የለም። መጠየቅ የሚኖርብን ምን ዐይነት ሰዎች ሆነን ብንፈጠር ነው እልክ ውስጥ ገብተን የተጠፋፋነውና የምንጠፋፋው? ብለን ነው። ለመሆኑ ትግል ብለው የጀመሩ ድርጅቶች ወይም ሰዎች ስልጣን ከመያዝ ባሻገር ሌላ ዓላማ ነበራቸው ወይ? ፖለቲካ የሚባለውንስ ፅንሰ-ሃሳብ በሚገባ ተረድተዋል ወይ? ወይስ የሚረዱ ናቸው? ከዚህም ባሻገር በጎናቸው ያሰለፏቸው ታጋዮችና ነፃ ልናወጣህ ነው የምንታገለው ይሏቸው የነበሩና አሁንም የሚከተሏቸውን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ፍላጎታቸውንና ህልማቸውን በእርግጥ ያውቃሉ ወይ? በእርግጥስ በሚያራምዱት የትግል ስልት ለሚከተሏቸውና ለህዝባቸው ዕውነተኛውን ነፃነት ሊያጎናጽፏቸው ይችላሉ ወይ?

ስለሆነም በትግልና በፖለቲካ ስም የተደረገውን መጠፋፋት ስንመረምር ትግል የሚባለው ነገር በደመ-ነፍስ የተመራ ወይም ሙሉ በሙሉ ድንቁርናነት የተሞላበት ነው ማለት ይቻላል። አንዳች ዐይነት ፍልስፍና ወይም መመሪያ የሌለው ፖለቲካ ፖለቲካ ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ፖለቲካ የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ ወይም በፖለቲካ ስም የሚካሄድ ትግል በጥቁርና በነጭ እየተጻፈ የእኔን ሃሳብ ያልተቀበለ ወይም እኔ በምለው የማይመራ ጠላቴ ነው በማለት መግደያ ወይም አንድን ሰው ማስወገጃ መሳሪያ ባለመሆኑ ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አንድ ወጥ አስተሳሰብ የሌለውንና ሊኖር የማይችለውን ያህል ፖለቲካ ራሱም በቅራኔዎች የተወጠረና በተለያዩ ሰዎች እንደየሁኔታው የሚተረጎም ነው። ይሁንና አንድ ዐይነት የፖለቲካ ግንዛቤ ለማግኘት ወይም በአንዳች ዐይነት ርዕይ ለመመራት ከተለያዩ የፖለቲካ ቲዎሪዎች ጋር መተዋወቅ ያስፈልጋል። ይኸኛው ነው ትክክለኛውና የህብረተሰቤንም ችግር ሊፈታ የሚችለው ቲዎሪ ተብሎ በአንዳች ዐይነት የፖለቲካ ቲዎሪ ከታመነ የአንድን ህብረተሰብ ስነ-ልቦናና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማንበብ ወይም መተንተን ግዴታ ነው። በሌላ ወገን ግን በሳይንስ ወይም በፍልስፍና ዓለም ውስጥ የአንድን ህብረተሰብ ሁኔታ በደንብ ለመመርመር የሚያስችሉ በጣም የተወሰኑ ሳይንሳዊ አካሄዶች ወይም የምርምር ዘዴዎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ተግባራዊ ሊሆንና ችግርን ሊፈታ የሚችል ፕሮግራም መንደፍ ይቻላል።

ለማንኛውም በአገራችን ምድር በብሄረሰብ ስምም ሆነ በብሄራዊ ደረጃ ተደራጅተው በፖለቲካ ስም ትግል ሲያካሂዱ የከረሙና አሁንም ቢሆን ትግል እናካሂዳለን የሚሉ፣ ስልጣንም ጨብጠው 27 ዓመታት በሙሉ ህዝባችንን ፍዳውን ሲያሳዩት የከረሙትንና፣ የኤርትራን ሁኔታ ስንመለከትና፣ ከሁለት ዐመት ተኩል ጀምሮ ስልጣን የጨበጠውን የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ፖለቲካ ስንመረመር እነዚህ ሁሉ ኃይሎች በደረጃ ቢለያዩም ሁሉም ቢሆኑ በደመ-ነፍስ የሚመሩት ወይም ደግሞ ፖለቲካቸው በከፍተኛ ደረጃ ከዕውቀት ጋር ያልተያያዘ መሆኑን ተጨባጩ ሁኔታ ያረጋግጣል። ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት በመስጠት ሌላውን ማሳመን አያስፈልግም። ምክንያቱም የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ህዝባችን የሚኖርበት አሳዛኝ ሁኔታ፣ መፈናቀሉ፣ ዲሞግራፊ ለመለወጥ የሚደረገው የመሬት ወረራ፣ ቅጥ ያጣና አረመኔያዊነት የተሞላበት ግድያ፣ ቤተክርስቲያናትን ማቃጠልና የሃይማኖት መሪዎችን መግደልና የተቀሩትን ምዕመናን ማሳደድና ማሰቃየት፣ የቢሮክራሲው አድካሚነት፣ የመንገዶቻችንና የቤቶች አሰራሮች፣ በህጻናትና በታዳጊው ወጣት ላይ የሚደርሰው ግፍ፣ የፍርድቤትና የፖሊሶች ማንአለኝበት፣ ሰው ሲገደል ዝም ብሎ መመልከት፣ ወንጀለኛውን ትቶ ወንጀለኛ ያልሆነውንና ለመብት የሚታገለውን ማሰቃየትና ወደ ወህኒቤት መወርወር፣ የአገዛዙ ህሊና-ቢስነት ወይም ርህራሄ ማጣት… ወዘተ. … ወዘተ. እነዚህ ሁሉ በቂ ምስክሮች ናቸው። ከዚህም በላይ በግልጽ አማራ በሚባለው ብሄረሰብና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችና በተቋማቱ ላይ ዘመቻ ማድረገና እንደዋና ጠላት ማየት፣ ሰሞኑን እንደምናየው ደግሞ የመስቀልን በዓል ማክበር አትችሉም፣ አማራ የሚባሉት ደግሞ ዲሞግራፊ ትለውጣላችሁ በመባል ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የሚደረገው ዕገዳ፣ ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ታሪክና አገነባብ በሚገባ አያውቁም ማለት ነው። ካለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ባህላዊና የዕውቀት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እዚህ ደረጃ ላይ ባልደረሰች ነበር።  የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዋናው መሰረት የተጣለው በሰሜኑ የግዛት ክፍልና በተለያየ ጊዜያት ኢትዮጵያን ሲገዙ በነበሩ ነገስታትና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማካይነት ነው። በኋላ የመጡ ሃይማኖቶችና በዛሬው ወቅት የገዢው መደብ የሚያመልክበት የፔንጤ ቆንጤ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ያደረጉት ምንም ዐይነት አስተዋፅዖ የለም። እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ልክ እንደመንግስት ሃይማኖት መወሰዱ ወይም ደግሞ መንግስትና አገዛዙ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ መደጋገፋቸው የታሪክ ግዴታ የነበረ ነው። በሌላው ወገን ግን እንደዚህ ብዬ ሳትት የሌሎችን ሃይማኖቶች መኖር መቃወሜ ሳይሆን ሃይማኖትን የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ ማድረግ፣ ወይም የመንግስትን መኪና እቆጣጠራለሁ በማለት በአንድ ሃይማኖትና ጎሳ ላይ ያነጣጠረ ድርጊት መፈጸም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራን ይችላል ከሚለው ፍርሃት በመነሳት ነው። ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር ግን የጋራ ነው የሚለው መሰረተ-ሃሳብ በሁላችንም መንፈስ መቀረጽ አለበት። ስለሆነም ሃይማኖት የፖለቲካ መሳሪያ መሆን የለበትም። ፖለቲካ በገለልተኛ መልክ የሚካሄድ እንጂ የከፋፍለህ ግዛው መሳሪያ መሆን የለበትም። በመሰረቱ ይኸኛውም ሆነ ያኛው ሃይማኖት ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን የሚያስተምሩ እንጂ የቂም-በቀል መሳሪያ መሆን የለባቸውም። ሃይማኖትን የቂም-በቀል መሳሪያ የሚያደርጉና አንድን ብሄረሰብ የሚያስፈራሩ ወይም ከተወለደበት መንደርና ከተማ እንዲፈናቀል የሚያደርጉ በሃይማኖት የሚያምኑ አይደሉም። እንደዚህ ዐይነቱን ዐይን ያወጣ ድርጊት የሚፈጽሙ የክርስቶስን መልዕክት የሚያንቋሽሹ ናቸው። በመሰረቱ የእግዚአብሄር ጠላቶች ናቸው።

ለማንኛውም ዛሬ በህዝባችን ላይ የሚወርደው ሰቆቃና ግድያ የሚያረጋግጠው አገራችንና ህዝባችን የስልጣኔን ምንነት በተረዳ፣ ከጉልበት ይልቅ ሳይንሳዊ ክርክርንና ውይይትን በሚያስቀድም፣ ፖለቲካ ማለት ህዝባዊ ተሳትፎንና የህዝብን መደራጀት የሚያስቀድም መሆኑን በተገነዘበ፣ በጤናማ የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ በመመራት ሁለ-ገብ ዕድገትንና መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግና፣ በተዘጋጀና በተደራጀ ኃይል እንደማይመሩ ነው። ትላንትም ሆነ ዛሬ በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈው ህዝባችንን ፍዳውን የሚያሳዩትና አገር የሚያፈራርሱት፣ ፈላስፋው አንድሬ ግሉክስማን እንደሚያስተምረን ከስህተታቸው በፍጹም ለመማር የማይፈልጉና ሰው የሚነግራቸውን ለመስማት የማይሹ ናቸው። እነሱ የሚሰሩት ወንጀልና አገርን ማፈራረስ እንደ ወንጀል የማይቆጠር፣ ወይም ደግሞ አንድን ህዝብ ፍዳውን ለማሳየትና አገርን ለማፈራረስ ከእግዚአብሄር ፈቃድ የተሰጣቸው ይመስል ይህንን ድርጊታቸውን የሚቃወመውንና የሚሟገታቸውን እንደወንጀለኛ አድርገው በመቁጠር ወደ እስር ቤት የሚከቱ ናቸው። ሁሉንም ነገር በጭንቅላቱ በማቆም የሚመለከቱና ከዚያ ሁኔታ በመነሳት አንድ ዐይነት ውሳኔ ለመስጠት የሚከጅላቸው ናቸው። መጥፎ ድርጊታቸውን ለማመዛዘንና ዛሬ የሚሰሩት ወንጀል በተከታታዩ ትውልድ ላይም አሉታዊ ውጤት በማሳደር አዲስና የተሻለ ስራ ለመስራት እንቅፋት እንደሚሆን የማይረዱ ናቸው። ባጭሩ እንመራዋለን የሚሉትን ህዝብ እንደሰው የማይመለከቱና እያንዳንዱም ሰው ለመኖር ሲል የግዴታ ሰላም እንደሚያስፈልገው የማይገነዘቡ ናቸው። የሰውን ልጅ የመኖር፣ የመፍጠርና በሰላም አገርን የመገንባት መብት በፍጹም የማያውቁ ናቸው።

                     ዕውቀተ-አልባ ፖለቲካ በምን መልክ ነው የሚገለጸው?

   I can calculate the motions of the heavenly bodies, but not the madness of people.

                                                                                                 Isaac Newton (1720)

የድንቁርና ፖለቲካ የሚያካሂዱ በህሊናቸው የሚመሩ አይደሉም። መመሪያ ወይም ፍልስፍና የላቸውም። ፖለቲካ የሚባለውን ነገር በደመ-ነፍስ ነው የሚመሩት። ልብስ ለብሰው ከመሄድ በስተቀር ሰው መሆናቸውን የሚገነዘቡ አይደሉም። ስለሰው ልጅ ርህራሄ የላቸውም። ፍቅር የሚባል ነገር አያውቁም። በመግደል ብቻ ነው መንፈሳዊ ደስታን የሚጎናጸፉ ወይም የሚረኩ የሚመስላቸው። በማስፈራራት ብቻ ነው አገርን የሚገዙት። በራሳቸው ላይ ዕምነት የላቸውም። ይቀናቀነኛል ብለው የሚጠረጥሩትን አይ ያጠፉታል፣ አሊያም ደግሞ በሰበብ በአስባቡ እስር ቤት ውስጥ ይወረውሩታል። በመጥፎ ተግባራቸውም ትክክል ነው በማለት ይገፉበታል። በመጥፎና በጥሩ ድርጊት መሀከል ያለውን ልዩነት አይረዱም። ስለሆነም ስለጥበብና ልዩ ልዩ ባህላዊ ፈጠራዎች ስሜት የላቸውም።

ድንቁርናነት የተሞለባትን ፖለቲካ የሚያካሂዱ የራሳቸውን ታሪክ እንዳለ ይክዳሉ። ቀደም ብለው የተሰሩ ታሪኮችንና ካለማወቅ የተሰሩ ስህተቶችን በማናፈስ በአንድ ህዝብ መሀከል የማያስፈልግ ጥርጣሬና መፈራራት እንዲኖር ያደርጋሉ። የዛሬው ሁኔታ ካለትላንትናው ሊኖር እንደማይችል የሚረዱ አይደሉም። ታሪክ ተከታታይነት ያለውና ከአንዱ ትውልድ ወደ ሚቀጥለው መተላለፍ እንዳለበት አይገነዘቡም። ስለሆነም በአንድ ወቅት ከንቃተ-ህሊና ጉድለት የተሰራ ስህተትን በማራገብና በመዝናናት የተበላሸውን በተሃድሶ መንፈስ እያደሱ የተሻለ ታሪክን መስራት አይችሉም።  እነሱ የባሰ ወንጀልና አገር የሚያፈራርስ ስራ እየሰሩ ሶስት መቶና አራት መቶ ዐመታት ወደ ኋላ ተጉዘው በመሄድ በዚያን ዘመን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ነገስታትን ይወነጅላሉ፤ ያንቋሽሻሉ። የታሪክን ውጣ ውረድነት በፍጹም የሚገነዘቡ አይደሉም። የሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና በሂደት መዳበር እንደሚችልና፣ በተለይም የማቴሪያል ሁኔታዎች ሲለወጡ – ማለትም የከተማዎችና የመንደሮች ግንባታ፣ የስራ-ክፍፍል መዳበርና የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት፣ እነዚህን መልክ የሚያሲይዙ ባህላዊ ለውጦች መታየት… ወዘተ.- የማሰብ ኃይሉም በዚያው መጠን እንደሚዳብርና ነገሮችን ማገናዘብ እንደሚችል በፍጹም አይረዱም። ወደ ውስጥና ወደ ተለያየ አቅጣጫ የመመልከትና ነገሮችን የመመራመር ኃይል የላቸውም። በክርክር ወይም በውይይት አያምኑም። ክርክር ለጭንቅላት መዳበር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው አይገነዘቡም። የሌላውን አስተያየት ለመቀበል አይፈልጉም። ራሳቸውን ብቻ እንደአዋቂ ይቆጥራሉ። ለመቻቻል ቦታ የላቸውም። በመቻቻልና የሌላውን ሃሳብ በመቀበል ብቻ አንድ ጥሩ ነገር መስራት እንደሚቻል በፍጹም አይገባቸውም። ማንኛውም ነገር የብዙ ነገሮች ጥምር ውጤት መሆኑን በፍጹም አይረዱም። በአንድ ኢምንት ነገር ውስጥ እንኳ ሌሎች በጣም ጥቃቅን ነገሮችና የተለያየ ባህሪዎች ያላቸው ነገሮች እንዳሉ አይረዱም። ስለሆነም ማህበራዊም ወይም ህብረተሰብአዊ ዕድገት የብዙ ነገሮች ጭማቂ ውጤት መሆኑን አይገነዘቡም። ተፈጥሮም ሆነ ማንኛውም ህብረተሰብ በዲያሌክቲካል ሂደት በመጣመር ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላና ወደ ተሻለ እንደሚለወጡ በፍጹም አይገነዘቡም። በአንድ አገር ውስጥ የተሟላና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ሊመጣ የሚችለው የተለያዩ ነገሮችና ሃሳቦች ሲዋሃዱና ተቻችለው ሲኖሩ ብቻ መሆኑን አይቀበሉም። የሰውን ልጅ ውስጣዊ ኃይልና የተፈጥሮን ህግጋት በፍጹም አይረዱም። ተፈጥሮ የልዩ ልዩ ነገሮች ጥምር ውጤት መሆኗን አያውቁም። ተፈጥሮ ካለልዩ ልዩ አበባዎች፣ የዛፍ ዐይነቶች፣ ሰብሎች፣ ፍራፍሬዎች፣ ወንዞች፣ ተራራዎችና ሜዳዎች፣ ልዩ ልዩ ዐይነት እንስሳዎችና የዱር-አራዊት፣ …ወዘተ. ተፈጥሮ ልትባል እንደማትችል ሊገነዘቡ በፍጹም አይችሉም። ስለሆነም ተፈጥሮአዊ ንቃተ-ህሊና የላቸውም። የተፈጥሮ ትርጉም ስለማይገባቸው የብዙ መቶ ዐመታትን ዛፎች በእልክ ያወድማሉ። የሰው ልጅ ተፈጥሮን እንደሚፈልጋትና፣ ማንኛውንም ነገር ከተፈጥሮ ውስጥ እንደሚያገኝ አይገነዘቡም። የሰው ልጅ ምንነትና የመኖር ኃይሉ በተፈጥሮ የሚለገስ እንደሆነ በመንፈሳቸው ውስጥ የለም።

ስለሆነም ጭንቅላታቸው በድንቁርና የተናወጠ ፖለቲከኞች ነን ባዮች ለማንኛውም ነገር በድን ናቸው። አካባቢ ወደመ አልወደመ ስሜት የላቸውም። ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ኃላፊነት አይሰማቸውም። የአንድ አገር እሴትና የሰው-ልጅ ስነ-ልቦና እንዲወድም ሳያውቁት መንገዱን አመቻችተው ለውጭ ኃይሎች ይሰጣሉ። አንድን ታዳጊ ትውልድ የመጥፎ ባህሎች ሰለባ በማድረግ በዕድሜ እየገፋ የሚሄድ ሰው ወይም በዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች ተሸማቀው እንዲኖሩ ያደርጋሉ። የማይገባቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በአንድ አገር ውስጥ ተደራራቢና ተቆላላፊ ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ። የማነፃፀር ኃይል የላቸውም። በራሳቸው ህዝብና ምሁራዊ ኃይል ከመተማመን ይልቅ ለውጭ ኃይሎች ያጎበድዳሉ። በዚህም ዕውነተኛ የሆነ የአሽከርነት ባህሪያቸውን ያረጋግጣሉ። ሌላውም እንዲቀበል በማድረግ በአገራቸው ውስጥ ለውጭ ኃይሎች አጎብዳጅ ዜጋ የሆነ ኃይል እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

ጭንቅላታቸው በድንቁርና አስተሳሰብ የተወጠረ ታጋይ ነን ባዮች ስለ ዕድገትና ስልጣኔ ያላቸው ትርጉም የተጣመመ ነው። ኢኮኖሚዊ ዕድገትን ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ ከቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችና መንደሮች ነጥለው በማየት በትናንሽ ነገሮች ይኮራሉ። ህዝባቸው የተሟላ ኑሮ ኖረ አልኖረ ደንታቸው አይደለም። በጥራዝ ነጠቅ የአካዳሚክ ዕውቀት የተካኑም ስለሆነ በነገሮች መሃከል መተሳሰር እንዳለ በፍጹም አይገነዘቡም። ማርክ አውሬል(Marc Aurel)ከክርስቶ ልደት በኋላ ከ121-180 ዓ.ም የኖረው የሮማውያን ንጉስና ፈላስፋ እንዳለው፣ „የአካዴሚክ ዕውቀት ወደ አርቆ-አለማሰብ የሚጠጋ መንፈስን አይቀንሰውም፣ እንዲያውም አርቆ-አለማሰብ እየጠነከረና የበላይነትን እየተቀዳጀ እንዲሄድ ያደርጋል“ የሚለው ፍልስፍናዊ አነጋገር በእነዚህ ሰዎች ላይ ይንፀባረቃል። ስለሆነም ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይቆጠቡም። ጦርነት ይናፍቃቸዋል። ካለጦርነት የሚኖሩ አይመስላቸውም። በጦርነት ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ ሊኖር እንደማይችል በፍጹም አይረዱም። የጦርነት ዋናውም ስትራቴጂ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የተቻለን ነገር ሁሉ ማድረግ ነው የሚለውን የክላውዘቪትዝን አባባል በፍጹም አይቀበሉም። ሁልጊዜ በአሸናፊነት የሚወጡ ይመስላቸዋል። የአንድን አገር ታሪክና ባህል ካወደሙና ህዝብ ከተበታተነ በኋላ ተዝናንተው በመቀመጥ በአሽናፊነት የወጡ ይመስላቸዋል።

ባጭሩ የድንቁርና ፖለቲካን የሚያራምዱ የሳይንስን ትርጉምና ችግር ፈችነት በፍጹም አይረዱም። በዕውቀት የበላይነት በፍጹም አያምኑም። ከተፈጥሮ ጋር በመነጋገርና እየመላለሱ በመጠየቅ ብቻ ወደ ሚጠጋጋ መልስ ጋ ለመድረስ እንደሚቻል አይገነዘቡም። ስለሆነም የስልጣኔ ጠንቅ የሆኑና በአንድ አገር ውስጥ ያለ ህዝብ ተቻችሎ እንዳይኖር የሚያደርጉ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ስልጣን አካባቢ በፍጹም መደረስ የሚገባቸው አይደሉም። ፖለቲከኛ ነን እያሉ አስር ጊዜ ቢለፈልፉም ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሆነ፣ ለጥበብና ለባህላዊ ዕድገት የማያመች፣ ህዝቦች ተቻችለውና ተጋግዘው በጋራ አገራቸውን እንዳይገነቡ የሚያደርግ ፖለቲካ ስላልሆነ፣ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ፣ በፖለቲካ ስም የሆነ ያልሆነውን የሚዘላብዱ ከፖለቲካ መድረክ መገለል አለባቸው። ይህ ዐይነቱ ፖለቲካ የ27 ዓመቱን የወያኔ ማፊያዊና የጥፋት ፖለቲካ ያስታውሰናል። በመሰረቱ የህውሃት ሰዎችና ተከታዮቻቸው እንዳሉ ወህኒቤት መወርወርና ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው ናቸው። የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር የሆኑት ዶ/ር አቢይ ከአንድ ዐመት በፊት ባህርዳር ላይ ቤአዴን መሪዎች ጋር ተሰብስበው ንግግር ሲያድርጉ፣ „እኛ ኢትዮጵያውያኖች ይቅርታ መደራረግ አናውቅም“ ያሉት የሚያረጋግጠው እኚህ መሪያችን አገር ቤት ውስጥ 27 ዐመት ምን እንደተካሄደ አልተገነዘቡም ማለት ነው። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም እንዲሉ ህዝባቸን ግን ወያኔዎችና ግብረ-አበሮቻቸው የሰሩትን ግፍ መዝግበዋቸዋል።

ከላይ የተተነተነው ሀተታ የወያኔ ባህርይ ብቻ አይደለም። በደረጃ ይለያይ እንጂ በአገራችን ውስጥ በፖለቲካ ስም ይንቀሳቀሱ የነበሩትንና አሁንም የሚንቀሳቀሱትንም የሚመለከት ነው። ሻቢያና ኦነግ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ወጣቶችን የእሳት ራት ያደረጉ ሁሉ የዚህ ዐይነቱ የድንቁርና ሰለባ ናቸው። ራሱ ደርግና በተለይ እነኮረኔል መንግስቱና ሌሎች በአረመኔነታቸው ይታወቁ የነበሩ የሰራዊቱ አባሎችና የሲቪል አጋሮቻቸው ወጣቱን የዚህ ወይም የዚያኛው ድርጅት አባል ነህ በማለት ካለምንም ርህራሄ ረሽነዋቸዋል። የያዟቸውን ወይም እጃቸውን በፍላጎት የሰጡትን አስተምሮ እንደገና ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው መልካም ስራ እንዲሰሩ ከማድረግ ይልቅ እንዳለ ነው የረሽኗቸው። በዚህ ዐይነቱ ድርጊታቸው ምን አገኙ? አገሪቱን በምሁር ከማራቆት በስተቀር ምን ዐይነት ትርፍ አገኙ?

ከዚህ ስንነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን ምንም ነገር ሳይገባንና በእልክና በማናለኝበት ስሜት ብቻ በመወጠር አገራችንን አፍራርሰናል። በቅርብ የወጣው የኢንተለጀንስ መለኪያ የሚያረጋግጠው ይህንን ዐይነቱን ድርጊታችንን ነው። ማሰብ ብንችል ኖሮ እንደዚህ ዐይነት ውጥንቅጥ ውስጥ ገብተን ተጨራርሰን የመጨረሻ መጨረሻ አገራችንና ህዝባችንን ለሌሎች ጭራቆችና ባህለ-ቢስ ኃይሎች ባላስረከብን ነበር። ዛሬም ቢሆን ከዚህ ትምህርታችን የተማርን አይመስልም። ከምሁራዊ እንቅስቃሴና ሰፋ ካለ ጭንቅላትን ከሚያዳብር ስራ ይልቅ ባልባሌ ነገሮች በመጠመድ አሁንም ለሌላ ፍልሚያ የተዘጋጀን እንመስላለን። በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ስልጣንን በጨበጡ ሰዎች ወይም በመንግስት አማካይነት አይደለም። ፍልስፍናና ሳይንስ፣ ስነ-ጽሁፍና አርኪቴክቸር፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ባህላዊ ክንውኖች ከመንግስት መኪና ውጭ በግለሰቦች አማካይነት የተፈጠሩና የዳበሩ፣ እንዲሁም የተስፋፉ ናቸው። መንግስታት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ በግፊት የሚመጡ እንጂ በራሳቸው ጭንቅላት በማሰብ አይደለም። ስለሆነም በአገራችን ምድር ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ከፖለቲካና ከመንግስት መኪና ባሻገር ማሰብና እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን። ፖለቲከኛ ነን ባዮችና መንግስት ሰፋ ባለ ምሁራዊ ኃይል ትርጉም እንዳይኖራቸው ማድረግ አለብን። ሰፋ ያለ በምሁራዊ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ የሲቪል ማህበረሰብ ሲኖርና ተቋማት ሲዳብሩ መንግስት የሚባለውንና ፖለቲከኛ ነን ባዮችን ቦታ ማሳጣት ይቻላል። ወይም ደግሞ በምሁራዊ ኃይል አስጨንቆ በመያዝ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል።

ይህንን ካልኩ በኋላ በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የብሄረሰብ አርማን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ወይም ይህንን ወይም ያኛውን ብሄረሰብ እወክላለሁ የሚሉ በሙሉ በህግ መከልከል አለባቸው። ለግለሰብ ለነፃነት፣ ለሪፓብሊካን አስተሳሰብና ለዕድገት፣ እንዲሁም ወንድማማችና እህትማማች ህዝብ አንድ ላይ ተባብሮ አንድ ቁም ነገር እንዳይሰራ የሚያግዱ ናቸው። ፀረ-ስልጣኔና የባህላዊ ለውጥ ጠንቆች ናቸው። አብዛኛዎቹ ምንም ዐይነት ሰፋ ያለ የዕውቀት መሰረት ሳይኖራቸው ወጣቱን የሚያሳስቱ ናቸው። የብዙዎችም ዲግሪ የሚያጠያይቅና፥ ዲግሬ ጨብጠናል ካሉም ባኋላ ሳይንሳዊ ጽሁፍ በማቅረብ ሲያስተምሩ አይታዩም። የማሰብ ኃይላቸው በጣም ጠባብና በተወሰኑ ኢ-ሳይንሳዊ በሆኑ ጽንሰ-ሃሳቦች ላይ ብቻ የሚሽከረከሩ ናቸው። ለፋሺዝምና ለጭቆና አስተዳደር የሚያመቹና አንድ ጥቁር ህዝብ የራሱን ስልጣኔ እንዳይሰራ የሚያግዱ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ተፈጥሮና ፀረ-ሳይንስ የሆኑ ኃይሎች ከፖለቲካ መድረክ መወገድ አለባቸው። የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን አገራችንና ህዝባችን በዘለዓለም ትርምስ ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርጉ ናቸው።

               የዛሬው የአገራችን ፖለቲካ ዘመናዊ ወይስ ዕውቀትን ያልተመረኮዘ ፖለቲካ!

የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ዶ/ር አቢይ „ታላቁን ሰው“  ሼክ አላሙዲንን ለማስፈታት ሳውዲ አረቢያ ሄደው ሲመለሱ ሚሊኒዩም ሁለት ሺህ አዳራሽ ውስጥ ዶ/ር ምህረት ደበበና ዘፋኙ አቶ ስለሺ ለወጣቶች በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ይጋብዟቸዋል።  በንግግራቸው ውስጥ „አዲሱ ትውልድ ዘመናዊ ፖለቲካን እንጂ ባረጀ አስተሳሰብ መመራት የለበትም“ ብለው ተናግረው ነበር።

በእርግጥ ዘመናዊ ፖለቲካ ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ቢያንስ የሰለጠነ ፖለቲካ ማለታቸው እንደሆነ ልንገምት እንችላለን። ዘመናዊ ወይም ተራማጅ አስተሳሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በግሪክ ሶፊስቶች የፈለቀ ሲሆን ከትራዲሽናል እሴቶች በመላቀቅ ለክርክርና ለተራማጅ አስተሳሰብ ክፍት ማድረግ ማለት ነው፤ በጊዜው ሰፍኖ የነበረውን ሁኔታ ማሻሻል ወይም መለወጥ ማለት ነው። እነ ሶክራተስና ፕላቶ እንዲሁም የእነሱን ፈለግ የተከተሉ ሲነሱ ለጭንቅላት ከፍተኛ ቦታ በመሰጠት ለሁለ-ገብ ለውጥና ሚዛናዊ ዕድገት የግዴታ አርቆ-ማሰብ(Rational  Thinking) አስፈላጊ መሆኑና ዕውቀት የሚባለው በክስተት ላይ የሚመሰረት ሳይሆን ከጭንቅላት የሚፈልቅና በሃሳብ ላይ የሚመሰረት መሆኑን ያሰምሩበታል። የካቶሊክ ሃይማኖት ከፊዩዳሊዝም ጋር በመጣመር በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከ600 ዓ.ም እስከ 13ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ሲገዛ ለኋላ-ቀርነት፣ ለሳይንስና ለፍልስፍና ዕድገት ተቀናቃኝ፣ ለድህነትና ለበሽታ ምክንያት መሆኑን የተረዱ ምሁራን ደግሞ ከፍተኛ ትግል በማድረግ የፊዩዳሊዝምን አገዛዝና የካቶሊክ ሃይማኖትን ርዮተ-ዓለምን አሽቀንጥረው በመጣል ለግልጽ አስተሳሰብ፣ ለግለሰብ ነፃነትና ለሪፓብሊካን  አገዛዝ መንገዱን ያመቻቻሉ። ይሁንና የገበያ ኢኮኖሚ ቀሰ በቀስ ተግባራዊ እየሆነ ሲመጣ ውክልናዊ አገዛዝንና የገበያን ኢኮኖሚ ብቻ ያስቀደመ የዘመናዊነት ፖሊሲ ተግባራዊ እየሆነ ይመጣል። ይህም የሚያመለክተው በመጀመሪያው ወቅት በእነሶክራተስና ፕላቶ የተፈጠረው የዘመናዊነት ወይም የዕድገት አመለካከት(Progressive Outlook) በማሰብ ኃይል ወይም በአርቆ-አሳቢነት ላይ የተመረኮዘና ሁሉንም ነገር የሚያካትት ሲሆን፣ የኋላ ኋላ የፈለቀው የገበያን ኢኮኖሚንና ሊበራሊዝምን ያስቀደመው በክስተት ላይ የሚያተኩርና፣ ከዚህ በመነሳት አንድን ነገር መተንተንና መረዳት ይቻላል ብሎ የሚያምን ነው። የመጀመሪያው በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ የሚያስተምር ሲሆን፣ የገበያ ኢኮኖሚና የሊበራሊዝም አስተሳሰብ እያንዳንዱ ነገር በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖርና፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ምንም ዐይነት ተፅዕኖ ማድረግ እንደማይችል የሚገልጽ ነው። ሁለት ዐይነት የዘመናዊነት አስተሳሰብ አለ ማለት ነው። ከዚህም ባሻገር የሶክራተሱና የፕላቶኑ መንገድ የግዴታ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ፍትሃዊነት እንዲመጣ ከተፈለገ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ እራሳቸው ፈላስፋዎች መሆን አለባቸው ወይም በፈላስፋዎች መመከር አለባቸው ሲል፣ሊበራሊዝምንና የገበያን ኢኮኖሚ የሚያስቀድሙ መንግስት የሚባለው ነገር ከገበያው በመውጣት ሁሉም ነገር ለገበያው ተዋንያኖች መለቀቅ አለበት፣ የገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ባለው ኃይል አማካይነት ሁሉንም በመቆጣጠር በዚህ አማካይነት ሚዛናዊነትና ፍትሃዊነት መምጣት ይችላሉ ብለው ይሰብካሉ። በኋላ የተነሱት እንደ ካንት፣ ሄገል፣ ሺለር፥ ጎተና ሌሎች ፈላስፋዎችና ገጣሚዎች የእነሶክራተስንና ፕላቶንን አስተሳሰብ በመጋራትት አንድ መንግስትና መኪናው ጥበባዊ መሆን አለባቸው፣ጥበባዊ መንግስት ብቻ ዕውነተኛ ስልጣኔን ሊያመጣ እንደሚችል ያስተምራሉ። ስለሆነ ጭቆናን የሚያስቀድም ወይም በኃይል የሚያምን እንደመንግስት ሊቆጠር እንደማይችል ይናገራሉ።

ነገሩን ለማሳጠር ዘመናዊነት በተለያዩ ምሁራን ዘንድ የተለያየ ትርጉም ቢሰጠውም ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ሲሆን ወደ ውስጥ ያተኮረና(Inward-Looking strategy) ሁለ-ገብ ዕድገትን የሚያስቀድም ነው። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የዕድገት ፈለግ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ ዕድገት የሚባለውን ነገር ከንጹህ-የፍጆታ አጠቃቀም (Consumption Pattern) ጋር የሚያያዝና ከሁለ-ገብ ዕድገት ይልቅ በአንድ ነገር ላይ የሚያተኩርና ከዚያ በመነሳት(Growth-Pol) በአንድ የህብረተሰብ ኃይል አማካይነት ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት (Trickle down effect)  የገበያ ኢኮኖሚ ሊመጣል ይችላል ብሎ የሚሰብክና የሚያስተምር ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የተኮላሽና የማሰብ ኃይልንና ዕውቀትን ያላስቀደመ የዘመናዊነት ፖሊሲ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካና በላቲንና በማዕከለኛው የአሜሪካን አገሮች ተግባራዊ በመሆን ለጭቆና አገዛዝ መስፈንና ለጥሬ-ሀብት ብዝበዛ ዋናው ምክንያት ሆነ። በተለይም በእነዚህ አገሮች የመንግስታት መኪናዎች ካለአግባብ መደለብና(Overdeveloped States) በጭቆና መሳሪያ መታጠቅ የዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሰና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አላግባብ ጣልቃ-መግባት ጋር የሚያያዝ ነው። በዚህ መልክ ከተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጋር ሳይሰተካከል እየደለበ የመጣ የመንግስት መኪና የካፒታሊስት መንግስታት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳዳግና መልክ ለማስያዝ የሚችሉበትን ፖሊሲ እንኳ ግንዛቤ ውስጥ እንዳይገባ ያገደና የቲዎሪና የፖሊሲ ክርክር እንዳይካሄድ መንገዱን የዘጋ ነው። ባጭሩ ዘራፊ መሰል የሆነ መንግስት(Predatory State) እንዲቋቋምና እንዲጠናከር የገፋፋ ፖሲ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ይህ ዐይነቱ በአሜሪካን ሶሲዮሎጂስቶችና ኢኮኖሚስቶች በቁንጹል መልክ ተተርጉሞ ለብዙ የሶስተኛው ዓለም አገር አገዛዞችና የፖሊሲ አውጭዎች የቀረበው የዘመናዊነት ፖሊሲና ፖለቲካ በየአገሮች ውስጥ የተስተካከለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ዕድገት እንዳይመጣ ለማገድ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ ለድህነት፣ ለብዝበዛ፣ ለጭቆናዊ አገዛዝና ለግለሰብ ነፃነት መታፈን፣ ላልተስተካከለ ዕድገት፣ ለቆሻሻ መጣያና ለሀብት ውድመት ዋናው ምክንያት በመሆን በተለይም አብዛኛውን የአፍሪካና የማዕከላዊና የላቲን አሜሪካ አገሮች ህዝቦች ፍዳቸውን እንዲያዩ በማድረግ ከአገሮቻቸው እየተሰደዱ እንዲሄዱ ለማድረግ የበቃ ፀረ-ፍልስፍናዊና ፀረ የሰው ልጅ ፖሊሲ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የዶ/ር አቢይ የዘመናዊነት ፖለቲካና ፖሊሲ የትኛው ዐይነት እንደሆነ በሰፊው አላብራሩም። የትኛውን ዐይነት ዘመናዊነትም ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይሁንና ግን የሁለት ዓመት ተኩሉን የዘመናዊነት ፖለቲካቸውን በምንመረምርበት ጊዜ ከዘመናዊነት ፖሊሲና ፖለቲካ በብዙ መቶ ሚሊዮን ማይሎች ርቆ የሚገኝ ወይም ደግሞ ፖለቲካው ወደ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን(Middle Ages) በከፍተኛ ፍጥነት ይዞን ወደ ኋላ የሚጓዝ እንጂ በተሀድሶ መንፈስ አዲስና ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን፣ እንዲሁም ደግሞ ህዝባችን በመፈቃቀርና በመከባበር እጅ ለእጅ ተያይዞ አንድ ጠንካራ አገርና ማህበረሰብ እንዲመሰርት የሚያደርግ አይደለም። የሁለት ዐመት ተኩሉ የዘመናዊነት ፖለቲካ የሚያረጋግጠው፣ ጽንፈኝነት የበዛበትና፣ ሰፊው ህዝባችን በፍርሃት የሚኖርበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዲፈናቀልና ሜዳ ላይ እንዲጣል የተደረገበት፣ ፋሺሽታዊ የኦሮሞ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከህውሃት ጋር በማበር አገሪቱን ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዲወረወሩ የተደረገበት፣ እንደነ ሺመልስ አብዲሳ የመሳሰሉ ፋሺሽታዊ ሰዎች በሚያስተዳድሩበት ክልል ሰዎች ሲገደሉና ሀብት ሲወድም ዝም ብለው የሚመለከቱበት፣ እነ ታከለ ኡማ የመሳሰሉ ዘመናዊ አራዳዎች ወጣቱን እያታለሉና የደሀውን ቤት እያፈራረሱ ሜዳ ላይ የሚጥሉበትና፣ የዲሞግራፊ ለውጥ ማድረግ አለብን በማለት ኦሮሞዎችን  ከየቦታው በማምጣትና አዲስ አበባ ላይ በማስፈር ልዩ ዐይነት በቀላሉ መቆጣጠር የማይቻል ህብረተሰብአዊ ክስተት መፍጠር፣ ከታች ወደ ላይ የሚያድግ(Organic Growth)የስራ-ክፍፍልና ማህበራዊ ዕድገት እንዳይኖር የሚያደርግ አደገኛ ዕድገት መከተል… ወዘተ. … ወዘተ. ናቸው የዶ/ር አቢይ አህመድና የገዢው መደብ የዘመናዊነት ፖሊሲ። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ህዝባችንን የሚያገልና በቀጥታ ወደ ባርነት ኢኮኖሚ እንዲያመራ የሚያደርግና ኢንቬስተሮች ለሚባሉ ለውጭ ኃይሎች በሩን ከፍቶ የሚሰጥ አካሄድ ነው። ባጭሩ ይህ ዐይነቱ „የዘመናዊነት ፖሊሲ“፣ ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ፣ መንፈሳዊነትንና ሃሳብን የሚያስቀድም ሳይሆን ጎጠኝነትን ያስቀደመ፣ የአገር ሀብት እንዲወድም የሚያደርግና ባጠቃላይ ሲታይ ለሁለ-ገብ ዕድገት የማያመችና ድህነትንና ረሃብን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከአገራችን ምድር እንዲወገድ የሚያደርግ  የዘመናዊነት አካሄድ አይደለም። የኢኮኖሚ ፖሊሲውንና በየጊዜው የሚወሰደውን ብድር በምንመለከትበት ጊዜ ፖሊሲው የባሰ ወጥመድ ውስጥ የሚከተን ነው። በሌላ ወገን ግን ዶ/ር አቢይ እየመላለሱ የሚነግሩን ነገር አለ። ይኸውም „ኢትዮጵያን እንደ አውሮፕያውያን አገሮች ማሳደግና ውብ ውብ ከተማዎች  መገንባትን እመኛለሁ፣ ወይም ምኞቴ  ኢትዮጵያችን እንደ አውሮፓ አገሮች እንድትሆንልኝ  ማድረግ ነው“ የሚል ነው። የተለያዩ አውሮፓ አገሮች የተለያየ የህብረተሰብ ታሪክ ቢኖራቸውምና እንደ ጀርመን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ የመሳሰሉት የዳበረ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ቢኖራቸውም፣ የከተማዎችን አገነባብ ስንመለከት በአብዛኛው የአውሮፓ አገሮች የከተማዎችና የመንደሮች አገነባብ አነሰም በዛም ተመሳሳይነት አለው። ዶ/ር አቢይ አገሬ እንደ አውሮፓ አድጋ ማየትን ነው የምመኘው ሲሉ ከአውሮፓው የህብረተሰብ ታሪክና ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር ትውውቅ ይኑራቸው አይኑራቸውም ማወቅ አይቻልም። ይሁንና በምኞትና በተግባር መሀከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ግልጽ ነው። ለማንኛውም ዶ/ር አቢይ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲን እያካሄዱና፣ እንደነሺመልስ አብዲሳ የመሳሰሉት የክልል አስተዳዳሪዎች በህዝባችን ላይ ጦርነት ከፍተው ህዝብ በሚያፈናቅሉበትና ሰላም ባልሰፈነበት አገር እንዴት ተደርጎ ካፒታሊዝም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም። ለካፒታሊዝም ዕድገት የመንፈስ ተሃድሶና ሀቀኝነት፣ እንዲሁም ቆራጠኝነት በጣም ወሳኝ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሰላም ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በሶስተኛ ደረጃ፣ የህዝብ ተሳትፎንና በራስ መተማመንን ይጠይቃል። በአራተኛ ደረጃ፣ መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ማነቆ መላቀቅ አለበት። በአምስተኛ ደረጃ፣ ሁለ-ገብ ዕድገትን ሊቀይሱና ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉ አገር ወዳድ የሆኑ ኃይሎችን መሰብሰብና ኃላፊነት መስጠት ያስፈልጋል። በስድስተኛ ደረጃ፣ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ድህነትን ማጥፋት ነው። ድህነትን ሳያስወግዱ ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ መሸጋገር በፍጹም አይቻልም። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ጠግቦ ሲበላና አስፈላጊውን ዲዬት ሲያገኝ የመስራት ፍላጎቱና ጥንካሬ ይኖረዋል። በስድስተኛ ደረጃ፣ በብሄረሰብ ላይ ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልላዊ አስተዳደር ለካፒታሊዝም ዕድገት እንቅፋት ነው። የሰው ኃይልና ካፒታል በአንድ አገር ውስጥ እንደልባቸው መንቀሳቀስ በማይችሉበትና የአገር ውስጥ ኢንቬስተሮች በአንዳንድ የክልል አስተዳዳሪዎች ከሌላ አገር ከመጡ ኢንቬስቶች በታች ዝቅ ተብለው በሚታዩበት አገርና እንደልባቸው ሀብታቸውን ኢንቬስት ለማድረግ በማይችሉበት አገር የውስጥ ገበያን ማሳደግና ለካፒታሊዝም መሰረት መጣል አይቻልም። እነዚህና ሌሎች አያሌ ነገሮች ሊሟሉ በማይችሉበት አገር እንደ አውሮፖው ዐይነት ዕድገት መመኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ከማውራት ወይም አልኩኝ ከማለት በስተቀር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም።

ወደ ፖለቲካውም ስንምጣ ማንኛውም ድርጅችትና ፓርቲ በየቦታው እንደልቡ እየተዘዋወረ ቅስቀሳ ለማድረግ የማይችልበትና የአገዛዙ ፖለቲካ በስይስተማቲክ ጭቆና ላይ የተሰማራና፣ ፍርድ ቤቶችና የፖሊስ መዋቅሩ በጽንፈኛ ኃይሎች፣ በትዕቢተኞችና በቂም-በቀለኞች የተያዘበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ስለሆነም በዶ/ር አቢይ የዘመናዊነት ፖለቲካ ዘመን ሁኔታው የባሰ ውስብስብ እየሆነ የመጣ ነው። ስርዓቱ ግልጽነት የሌለበትና ከፊዩዳላዊ ስርዓት ጋር ሲወዳደር እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ሆኖ እናየዋለን። ይህ ዐይነቱ አባባል ያለፈውን አርባ ዐመት በፖለቲካ ስም የተካሄደው የሚዘገንን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በፊዩዳሊዝም ዘመን የተሻለ ነፃነት ነበረው ብሎ መናገር ይቻላል። በደፈናው በማንም ኃይል አይገደልም፤ ወይም ማስፈራሪያ አይደርስበትም ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ከፊዩዳላዊ ስርዓት ከተላቀቀ በኋላ ወደ ዲሞክራሲያዊና የነፃነት ሰርዓት ስር ከመግባቱ ይልቅ ዘመናዊ ትምህርትን በቀሰሙ ኃይሎች ፍዳውን እንዲያይ ተደርጓል። ዘመናዊ የሚባለው ትምህርት፣ በአለባበስ እድናሸበርቅና ሌላውን እንድንንቅ፣ ሜርቼዲስና ቤኤምደብሊዩ የመሳሰሉ መኪናዎችን በመንዳት እንድንደላቀቅ፣ በስማርትፎን በመጠቀም ዘመናዊ እንድንመስል ከማድረግ በስተቀር መንፈሳዊ ተሃድሶን አላለገሰንም፤ ርህሩሆችና ዕውነተኛ ስልጣኔን አምጭዎች አላደረገንም። አረመኔዎች፣ ከሃዲዎችና አገር አፍራሾች አደረገን እንጂ።  ይህ ለምን እንደሆነ ልዩ ዐይነት ምርምርና ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ይሁንና ግን ነገሩን ባጭሩ መረዳት ይቻላል። ከዕውነተኛውና ከሳይንሳዊው፣ መንፈስን ከሚያጎለመሰውና ኃላፊነት እንዲሰማን ከሚያደርገው ከሶክራተሳዊ፣ ከፕላቶናዊ፣ ከስቶይኮችና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በሬናሳንስ ምሁሮችና፣ በጀርመን አዲያሊስቶች በፈለቀው ዕውቀት ጭንቅላታችን ባለመኮትኮቱና ከእንደዚህ ዐይነቱ ዕውቀት ጋር ባለመተዋወቃችንና ለመተዋወቅም ባለመፈለጋችን ነው። በተጨማሪም የእንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ መስፈን በአገራችን ምድር ያለውን የምሁራዊ ድክመት ሁኔታና አድርባይነቱን የሚያረጋግጥ ነው። ግልጽና ምሁራዊ ኃይል፣ እንዲሁም የሲብል ማህበረሰብ በሌለበት አገር እንደነዚህ የመሳሰሉ አገዛዞች እንደፈለጋቸው መፈንጨት ይችላሉ። ሜዳውን በሙሉ በመያዝ ያስፈራራሉ። ተግባራዊ የሚያደርጉትን የተበላሸ ፖሊሲ ትክክል ነው ብለው በማመን በዚያው ይገፉበታል። ስለሆነም ሌላና እልክ አስጨራሽ የሆነ የትግል ምዕራፍ ውስጥ እንድንገባ ያስገድዱናል። በቀላሉ ሊፈታ የማይችል ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል ማለት ነው!!

                                                 መደምደሚያ!!

ዛሬ በአገራችን በግልጽ የሚታየው ሁኔታ የጠቅላላው ህብረተሰብ ድክመት ነፀብራቅ ነው። በሀገር-አቀፍ ደረጃ የነቃና የተደራጀ ኃይል በሌለበት አገር ሰፊው ህዝብ ግራ መጋባቱ አይቀርም። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ መስክና በብሄራዊ ነፃነት አኳያ በጉልህ የሚታየውን ድክመትና የህዝባችንን አኗኗር ሁኔታ በየጊዜው አመርቂ በሆነ መልክ እያተተ በአንድ በኩል ህዝቡን የሚያስተምር፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገዛዙን የሚጋፈጥ ኃይል ባለመኖሩ አገዛዙና ጊዜው የኛ ነው ብለው የሚፈነጩ ኃይሎች የፈለጋቸውን ያደርጋሉ። ጠቅላላውን ህዝብ የሚጎዳና አገሪቱን ወደ ባሰ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ የሚከታት ፖሊሲ በመከተል ለማንኛውም ኃይል አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራሉ። በአገራችን በጉልህ የሚታየው ምሁራዊ ክፍተትና ዳተኝነት የውጭ ኃይሎች በአማካሪነት ስም እየመጡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቱን ከህዝቡ ፍላጎትና ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም፣ እንዲሁም ደግሞ ችግርን የማይፈታ ፖሊስ ተግባራዊ እንዲሆን በመገፋፋት የአገራችንን ሁኔታ የባሰውን ውስብስብ እያደረጉት ነው።  ይህንን ክፍተት በመገንዘብ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ በተጨባጭ የሚታየውን ሁኔታ ከሳይንስ፣ ከፍልስፍናና ከቲዎሪ አኳያ እየተነተነ ለማቅረብ ተስኖት ይገኛል። በተለይም በውጭ ኃይሎች የሚሸረብንን ሴራ በመከታተልና ሰፊ ምርምር በማድረግ ጥናታዊ ጽሁፍ ከማቅረብ ይልቅ እንዲያውም ይባስ ብሎ አገራችንን እዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የከተቷን ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ይማፀናል፤ የአገራችንና የህዝባችን ዕድል በእነሱ እጅ ያለ ይመስል በየጊዜው አቤቱታውን ያቀርባል። በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፌአለሁ የሚለው ኃይል ሃቁን ለመጻፍ የተዘጋጀ ባለመሆኑ ወይንም ደግሞ ከሳይንሳዊ የአተናተን ዘዴ የራቀ በመሆኑ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ወጣት እያሳሳተው ነው።

አብዛኛው ወጣት ደግሞ ከዕውቀት ዓለም የራቀና ለመማርና ለማወቅ ዝግጁ ባለመሆኑ በተለይም በዩቱብ ቻናሎች በሚሰለች መልክ የሚቀርበውን „ዜናና“ የስድብ ጋጋታ በመከታተል እንደዚህ ዐይነቱ እንካ ስላንቲሃ የፖለቲካ ትግል ስለሚመስለው በዚህ እየተዝናና ይኖራል። ሌላው ደግሞ የዚኸኛው ወይም የዚያኛው የፖለቲካ ድርጅትና የመንግስት ደጋፊ በመሆን ካለምንም ዕውቀት የካድሬነት ባህርይ በማሳየት በዕውቀት ወይም በሳይንስ ላይ የተመረኮዘ የሰከነ ውይይትና ጥናት እንዳይካሄድ ለማድረግ በቅቷል። አንዳንዱ እንዲያውም ምሁርና ሳይንስ አያስፈልግም በማለት በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ ደረጃ የሚደረገውን የአንድን አገር ነባራዊና የአስተሳሰብ ሁኔታ በመመርመር መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችለውን አስፈላጊ ጉዳይ ሲያንቋሽሽ ይታያል። አብዛኛው መጽሀፍ ጽፈህ አዘጋጅተህ ስትሰጠው ለመግዛት ቲያትር ሲሰራ ይታያል። በዕውቀት ላይ ኢንቬስት ለማድረግ በፍጹም አይፈልግም። ትንሽ አውቃለሁ የሚለውም ሳይንሳዊና ፍልስፍና የተሞላበት ዘመናዊ አስተሳሰብ ከማንፀባርቅና ወጣቱን ከማስተማር ይልቅ የባሰውኑ ወደዘመነ ፊዩዳሊዝም ሊወስደን ይፈልጋል። የሳይንስንና የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት በፍጹም አይረዳም። የአንድ አገር የመኖርና ያለመኖር፣ ከአንድ ትውልድ ወደ ሚቀጥለው የመሸጋገሩ ጉዳይ በጠንካራ ኢኮኖሚና ተቋማት ላይ መመስረት እንዳለበት በፍጹም የተገነዘበ አይመስልም። የአንድ አገርና ህዝብ ጥንካሬ ሰፊው ህዝብ በሚኖርበት የማቴሪያል ሁኔታ እንደሚለካ፣ በቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችና መንደሮች ግንባታና በሰፊው ህዝብ አኗኗር፣ በባህላዊ ዕድገት፣ ማለትም በስነ-ጽሁፍ፣ በቲያትር፣ በኮሜዲና በሙዚዬሞችና በሌሎች መንፈስን በሚያድሱ ነገሮች እንደሚመዘን በፍጹም ግንዛቤ የለውም። ስለሆነም ስለአገር መፈራረስ በሚያወራበት ጊዜ ስለምን እንደሚያወራ ግልጽ አይደለም። አብዛኛው ደግሞ ዝም ብሎ ባንዲራ ስላውለበለበና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስላለ ኢትዮጵያችን እንደ አገር ለመቆየት የምትችል የሚመሰው አለ። አገርና ህዝብ፣ የአኗኗሩ ሁኔታና ባንዲራ ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት እንዳላቸው በፍጹም አይገነዘብም። አንድ ህዝብ ቢያንስ መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘት አቅቶት ሲራብና ሲረገጥ እየታየ ስለባንዲራ ማውራት ምን ዐይነት ትርጉም ሊኖረው ይችላል? አንዳንዶች በሚያስቅ ሁኔታ ባንዲራና አገር ከህዝብ ይበልጣል እያሉ ይነግሩናል። በሌላ አነጋገር የአንድ አገር ህዝብ ተሟጦ ቢያልቅም ዋናው ነገር ሰው-አልባ አገር መኖሯና ባንዲራ መውለብለቡ ነው ዋናው ቁም ነገር በማለት አዲስ ፍልስፍና ያስተምሩናል። እስቲ አስቡት ሰው የሌለበት አገር ምን ዐይነት ትርጉም ይኖረዋል? እግዚአብሄር ተፈጥሮን ከፈጠረ በኋላ የሰው ልጅን የፈጠረው ካለምክንያት አይደለም። ምክንያቱም በእሱ አምሳያ የተፈጠረ ኃይል የማይኖርባት ተፈጥሮ ትርጉም ስለሌላት ነው። ስለሆነም አገርና ባንዲራ አገርነታቸውና ባንዲራነታቸው የሚረጋገጠው አንድ አገርና ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጅ ባላቤት ሲሆኑ ብቻ ነው። ለማንም የውጭ ኃይል የማይበገር አገር ሲኖርና ለሰፊው ህዝብ አስተማማኝ የሆነ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ሲገነባ የዚያን ጊዜም የባንዲራ ምንነቱ ብቻ ሳይሆን እናቶቻችንና አባቶቻችን የተዋደቁለት አገር በባንዲራ መልክ ይገለጻል። ይህንን ዐይነቱን እርስ በርሱ የተሳሰረ ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት ስንረዳና ያለ የሌለ ኃይላችንን በዕውቀት ላይ ስናውለው አዲስና የጠነከረች ኢትዮጵያን መገንባት ይችላል። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                         fekadubekele@gmx.de

https://www.youtube.com/watch?v=gj5zRx7G_cs

https://www.youtube.com/watch?v=jW7PHcuR570

 

Literature

Barry Jr. James, Measure of Science: Theological and Technological Impulses in Early

Modern Thought, Illinois, 1996

Engels, Frederick, Anti-Dühring, Peking, 1976

Fleck, Ludwik, The rise and development of a scientific reality, Germany, 2019

Gaarder, Jostein, Sofie`s World: History of philosophy written like a criminal roman,

München, 1998

Glucksmann, André, The Power of Ignorance, Stuttgart, 1985

Hutcheson, Francis, An Inquiry into the Original of Our Ideas of Beauty and Virtue,

New York, 1971

Jaynes, Julian, The Origin of Consciousness in the breakdown of the Bicamereal Mind,

Boston & New York, 2000

Kline, Morris, Mathematics and the search for Knowledge, New York, 1985

Korzybski, Alfred, Manhood of Humanity: The Science and Art of Human Engineering,

New York, 2017

Meštrović, Stjepan, The barbarian temperament: Towards a postmodern critical theory,

London & New York, 1993

Nicholas of Cusa, On Learned Ignorance, USA, 1985

Rescher, Nicholas, Process Metaphysics, New York, 1996

Seung, T.K, Plato Rediscovered: Human Values and Social Order, USA, 1996

Stankov, Georgi, The Universal Law through the Mirror of Philosophy,

Universal Law Press, 1999

Popper, Karl, The Open Society and its Enemies, London & New York, 2011

Popper, Karl, The Logic of Scientific Discovery, Great Britain, 1992

Trundle, Robert C, Ancient Greek Philosophy: it`s Development and relevance to Our

Time, Great Britain, 1994