[gtranslate]

 

ምን ዐይነት አገዛዝ በኢትዮጵያ ምድር ? ፋሺሽታዊ ወይስ ሌላ ዐይነት አገዛዝ ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

የካቲት 19፣ 2018

መግቢያ

እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ነፃነቶች የሚታፈኑ ከሆነ፣ አንድ ህዝብ በተለያዩ የሙያ ማሀበሮች የመደራጀት መብት ከሌለው፣ ሃሳቡን ለመግለጽ የሚችልበት መድረክ ከተነፈገው፣ በተለይም ደግሞ አንድ ግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ ተደራጅቶ ሀብትና ዕውቀቱን በመዋዕለ-ነዋይ መልክ ተግባራዊ እንዳያደርግ የሚነፈገው ከሆነና፣ በአጠቃላይ ሲታይ አንድ አገዛዝ በአንድ ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ የሚያካሂድ ከሆነ የዚህ ዐይነቱን አገዛዝ ይዘትና ባህርይ የመመርመሩ ጉዳይ በጣም አሰፈላጊ ነው። በተለይም ደግሞ አንድ አገዛዝ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ቀጥተኛ ድጋፍ በማግኘት በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ በተለያዩ መልኮች የሚገለጽ የዘር ማጥፋት እርምጃ የሚወስድ ከሆነና፣ በሃይማኖት ላይና በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ አገር እሴት ላይ ዘመቻ የሚያካሄድ ከሆነና የሰፊው ህዝብ አመለካከት እንዲዘበራረቅና እርስ በርሱ እንዲተላለቅ ማንኛውንም ተንኮል ነገሮች ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ፣ የዚህ ዐይነቱን አገዛዝ ባህርይ መመርመሩ ግዴታ ነው። ምክንያቱም ይህ ዐይነቱ አገዛዝ የተፈጥሮን ህግ በመፃረር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ጤናማ የሆነና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡ ውስጣዊ ኃይል እንዳያገኝ የሚሆን የማይሆን ተንኮል በመፍጠር ሃሞቱ እንዲፈስ ስለሚያደርግ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች ውስጠ-ኃይሉ እንዲሟጠጥ የሚደረግ ህዝብ፣ ወይም ደግሞ አትኩሮው ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲያመራ የሚገደድ ህዝብ አዳዲስ ሃሳቦችን ሊያፈልቅና ኑሮውን ሊያቅላሉ የሚችሉለትን መሳሪያዎችን መፍጠር አይችልም።

የዛሬው አገዛዝ ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ ይባስ ብሎ በቁጭትና በንዴት አገሪቱን ማመስና ንጹሃን ዜጎችን በአደባባይ ላይ በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛል። ማንኛውንም በጭንቅላት ውስጥ ያለውን የሞራል ገደብ በማስወገድ ካለምንም ይሉኝታ የዚህችን አገርና የህዝቦቿን ዕድል እኔና ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ብቻ ነን ልንወስን የምንችለው፣ እኛ የምናዘውንና ለማድረግ የምንፈልገውን ሁሉ የሚቃወም ካለ መጨፍጨፍና መደምሰስ አለበት በማለት አገሪቱን በማመስና ህዝቡን በማዋከብ ላይ ይገኛል። የዛሬውን የወያኔ አገዛዝ ድርጊት በሚመለከት ከተለያዩ ተቃዋሚ ነን ከሚሉ „ድርጅቶችም“ ሆነ የፖለቲካ ተዋንያን የሚሰጠው አስተያየት በአብዛኛው መልኩ እጅግ የሚያሳዝንና በማንኛውም የፖለቲካና የህብረተሰብ ሳይንስ ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ሳይንስ የሚመዘን አይደለም። አብዛኛዎቹ በድርጅት ደረጃ ተደራጀን የሚሉና፣ በግለሰብም ደረጃ አጋጣሚን በማግኝት ድምጻቸውን የሚያሰሙ የዛሬውን አገዛዝ ድርጊት አሳንሰው ነው የሚመለከቱት። እንዲያውም አንዳንዶቹ እንደሚሉትና ተራውን ሰው ለማሳመን የሚሞክሩ፣ የወያኔ አገዛዝ „ የችግሩ መንስኤ እራሱ ስለሆነ ፣ መፍትሄውም እሱ እጅ ውስጥ ነው ያለው “ ብለው እቅጩን ይነግሩናል። አንዳንዶች በምሳሌ በማሳየት ወያኔን እንደመፍትሄ አፍላቂ አድርገው ያቀርቡታል። በተለይም በታህሳስ 2፣ 2017 ዓም ብረሰልስ ላይ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ንግግር ያደረገ አንድ ግለሰብ እንደሚለው፣ እሱ ከመጣበት ብሄረሰብ ውስጥ አንድ ለአቅመ-አዳም ያልደረሰች ልጃገረድ በአንድ በጠና ሰው የምትደፈር ከሆነ የልጂቱ ቤተሰቦች የሚያቀርቡት መፍትሄ ልጃቸውን ለደፈራት ሰው በማጋባት ይገላገላሉ ይለናል። በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን ድርጊት በልጃቸው ላይ የሚፈጽሙ ቤተሰቦች ስተደፈርና ከተደፈረች በኋላ ምን ዐይነት የህሊና ቀውስ እንደሚደርስባት ሊገነዝቡ የሚችሉ አይደሉም። እዚህ አውሮፓ ውስጥና አሜሪካንም፣ ሴቶች ለአቅመአዳም ከመድረሳቸውም በፊትም ሆነ በኋላ የሚደፈሩ ከሆነ ዕድሜያቸውን በሙሉ ሲሰቃዩ እንደሚኖሩ ነው የተረጋገጠው። ከሚደርስባቸው የህሊና-ቀውስና በወንድ ላይ ከሚያጡት ዕምነት ለመፈወስ ሲሉ የብዙ ዐመታት በሳይኮሎጂስቶች ቴራፒ ይደረግላቸዋል። ይህንን ሃሳብ የሰነዘረው ወንድማችን ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማረ፣ ከዚያም በደርግ ጊዜ እንደሌሎች በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀድሞይቷ ሶቭየት ህብረት የተላከና፣ እዚያ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ አውሮፓ ውስጥ በመቅረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዋንያን ነን የሚሉ „ የ ተራድኦ “ ድርጅቶች ውስጥ በመቀጠር ከአርባ ዐመታት በላይ የሰራ ሰው ነው። በመሰረቱ እንደዚህ ዐይነቱ አሰተሳሰብና አባባል በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከተማረና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እዚህና እዚያ በመራውጥ የዓለምን ህዝብ የሚያዋክቡ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ ከሰራና „የስራ ልምድ ካካበተ“ የሚጠበቅ አይደለም። ውድ ወንድማችን እንደተማረ ሳይሆን እንዳልተማረ ሰው ሆኖ ነው የተሰበሰበውን ህዝበ-አዳም ለማሳመን የሚሞክር የነበረው።

በዚህ መልክ ባይሆን እንኳ፣ አገር ቤትም ሆነ ውጭ እንቀሳቀሳለን የሚሉ የየግለሰቦችንም ሆነ የድርጅቶችን መግለጫ በደንብ መሰመር ለመሰመር ላነበበ የዛሬው አገዛዝ የተቅዋም መሰረቱ ምን እንደሆነ ? በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም  እንደሚመራ? የሚከተላቸው „ የኢኮኖሚ ፓሊሲዎች “ ምን እንደሚመስሉና፣ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜም ምን ዐይነት ህብረተሰብአዊ አሉታዊ ውጤቶችን እንደሚያስከትሉ ? በደንብ የተከታተሉና የሚከታተሉም የሚመስሉ አይደሉም። ሌላው ትልቁ የታሪክ ወንጀለቻው ደግሞ፣ እነዚህ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ያገባኛል የሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ገለጻ ሲሰጡ ወይም አንዳች ሃሳብ ሲሰነዝሩ፣ የዛሬው የወያኔ ብቻውን የቆመና የሚፈጽማቸውም ወንጀሎች በሙሉ ከውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ አድረገው ነው የሚመለከቱት። በእነሱ ዕምነት የዛሬው የወያኔ አገዛዝ በዓለም አገዛዝ የጭቆናና የብዝበዛ ሰንሰለት ውስጥ የተካተተ አይደለም። ስለሆነም የውጭ ኃይሎች ድርጊቱን በጥሞና የሚመለከቱና ለኢትዮጵያ ህዝብም የሚያስቡና በወያኔ ድርጊትም የሚፀፀቱ ናቸው። የፖለቲካ ተዋንያን ነን የሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የወያኔ አገዛዝ ለምን እንደዚህ ዐይነት ውስብስብ ችግር እንደሚፈጥርና ሰውንም እንደሚጨፈጭፍም በደንብ አያስረዱንም። እንዲያው በደፈናው ችግሩን ራሱ ወይኔ የሚፈጥር በመሆኑ ከሱ ውጭ ወይንም እሱን ሳያካትቱ ችግሩን መፍታት አይቻልም ይሉናል። እነዚህ ኃይሎች ሳያውቁ አንድን ችግር መፍጠርና፣ አውቆ ችግርን በመፍጠር መሀከል ያለውን ልዩነት የተገነዘቡ አይመስለኝም። በተጨማሪም በእነሱ አመለካከት አንድ ስልጣንን የጨበጠ ኃይል የፈለገውን ሊያደርግ ይችላል፣ መንግስት የሚባለው ፍጡርም የማይነካ፣ የማይዳሰስና የማይወነጀል መሆኑን ነው አድርገው ሌላውን ለማሳመን የሚሞክሩት። በእነዚህ ተቀዋሚ ነን ባዮችና የሪል ፖለቲካ አራማጆች ዕምነትና ግንዛቤ በአንድ አገር የሚኖር ህዝብ ሊኖርና ሊያልም የሚችለው አንድ አገዛዝ ከላይ በሚወረወርለት ህግ መሰረት ብቻ ነው። በራሱ ተነሳሽነት ዕውነተኛ ነፃነትን በመቀዳጀት ታሪክን የመስራት መብት የለውም ይሉናል። ወይም ደግሞ አንድን አገርና ህዝብን የሚመለከት ህገ-መንግስት የግዴታ የህዝቡን ነፃነት ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ እንዳለበትና ጠንካራና ነፃ ኢኮኖሚ መገንባት እንዳለበት የሚቀበሉና የሚያምኑ አይደሉም።

ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ በምድር ላይ የሚታየውን ህሊናን የሚዘገንን ድርጊት እንደተራ ነገር አድርጎ ለማቅረብ መሞከር የግለሰቦችንም ሆነ የድርጅቶችን የሞራል ብቃትነት መኖርና አለመኖር የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፣ ታሪክንም ለመስራት እንደማይችሉ ነው የሚያረጋግጡት። ህዝባችን አልተማረም፣ ውጭ አገርም ተሰበጣጥሮ የሚኖረውም ኢትዮጵያዊ የመማር ዕድል ለማግኘት የቻለ አይደለም ተብሎ ከራስ ጥቅም አንፃር በመነሳት „የፖለቲካ ትንተናና ገለፃ“ የሚሰጥ ከሆነ የህዝባችንን ሰቆቃ ከማራዘምና አገዛዙን ከመጥቀም በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊኖረው በፍጹም አይችልም።  ስለሆነም ለፖለቲካ ነፃነትና ለስልጣኔ የሚደረገውን ትግል ትክክለኛ ፈር ለማሲያዝ የግዴታ የአገዛዙን ርዕዮተ-ዓለም፣ የሚመረኮዝበትን የጭቆና አወቃቀር፣ ማለትም የሚሊታሪውን፣ የፀጥታውንና የአፋኝ ኃይሉን፣ እንዲሁም የፖሊሱን ኃይል የግዴታ መመርመር ያስፈልጋል። በተጨማሪም እነዚህ የአገዛዝ መዋቅሮች በረቀቀ መልክ በዓለም አቀፍ አገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ በመካተት፣ በአንድ በኩል የፖለቲካ ነፃነትን አፋኝ እንደሆኑ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ድህነትንና ሀብረተሰብአዊ መዝረክረክ በከፍተናኛ ደረጃ እንዲመረቱና እንዲስፋፉ ማድረግ እንደተቻለ ለማሳየት እሞክራለሁ። ከዚያ በፊት ግን መንግስት ማለት ምን ማለት ነው ? የሚለውን በመጠኑም ቢሆን ላብራራ እሞክራለሁ።

መንግስት ማለት ምን ማለት ነው ? መሰረታዊ ተግባሩስ ምንድነ ነው ?

አምብሮጊዮ ሎሬንዜቲ የተባለው የ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጣሊያናዊ የሬናሳንስ ታላቅ ምሁር አንድ ጥሩ መንግስት በምን መልክ እንደሚገለጽና ተግባሩም ምን እንደሆን Allegory of Good and Bad Government በሚለው ጽሁፉ እንደሚቀጥለው ያትታል። “ አንድ ጥሩ መንግስት ህዝቡን ለማስደሰት ሲል ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችን ይገነባል ፤ ህዝቡ ስነ ስርዓት ያለው ኑሮ እንዲኖር የተቻለውን ነገር ያደርጋል። የዕደ – ጥበብ ሙያ እንዲያብብ፣ ቆንጆ ቆንጆ ሱቆች እዚህና እዚያ እንዲስፋፉና ህዝቡ በመተሳሰር የኑሮን ትርጉም እንዲረዳ ለአንድ አገር ዕድገት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ ተግባራዊ ያደርጋል ።  በሌላ ወገን ግን አንድ መጥፎ መንግስት አገርን በማፈራረስ ፣ በመዝረፍ፣ በመሰረርና በግድያ  የሚገለጽ ነው “ ፣ ይላል። ይህ ዐይነቱ የመጨረሻው አባባል የዛሬውን የወያኔን አገዛዝና በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚታወቁ አገሮችና በአሜሪካንም የተስፋፋውን የመንግስት ዐይነት ሁኔታ ያመለክተናል።   ይህ የአምብሮጊዮ ሎሬንዜቲ የመንግስት ፍልስፍና በ1338 ዓ.ም የተጻፈ ሲሆን፣ አቀራረቡ በጣም ተምኔታዊ ወይም ደግሞ አይዲያሊስቲክ አቀራረብ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ አቀራረብም በሌላ መልክ በግሪክ ፈላስፎችና የኋላ ኋላም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የህብረተሰብ አወቃቀር እየተወሳሰበ ሲመጣ አንድ መንግስት በምን መልክ መዋቀር እንዳለበትና፣ አንድ ህዝብስ በምን መልክ መተሳሳር እንዳለበት በተለያዩ ፈላስፋዎች ዘንድ በተለያየ መልክ ሲስተጋባ ቆይቷል። በተለይም አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ወደ ህብረ-ብሄር ሲያመሩ የታሪክ ግዴታ ሆኖ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት ወደ ውስጥ ያተኮረ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ ነው። በጊዜው በአንድ አገር ውስጥ  በኬላ ተካለው እዚህና እዚያ የሚገዙ የመሳፍንት አገዛዞች ሰፋ ላለ የገበያ ኢኮኖሚ እንቅፋት በመሆናቸው በጊዜው የተነሱት የፍጹም ሞናርኪዎች የግምሩክ ቀረጥን በማስወገድ በአንድ ኖርም የሚተዳደርና በአንድ ገንዘብ አማካይነት የሚካሄድ የገበያ ኢኮኖሚና ብሎም የንግድ ልውውጥ እንዲዳብርና እንዲስፋፋ ማድረግ ነው የጀመሩት። ይህ ዐይነቱ የአገርን የውስጥ ገበያ ማስፋፋቱና፣ አንድ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ ለካፒታሊዝም ዕድገት፣ እንዲያም ሲል ለካፒታልና ለስራ-ጉልበት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። አዳዲስና የነቁ ኃይሎች ብቅ እንዲሉና አዲስና ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለ ህብረተሰብ እንዲመሰርቱ አመቺ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ይሁንና ግን እነዚህ ኃይሎች የፊዩዳሊዝምን ኖርሞችና ስራ ጎታችነት ሊደመስስ የሚያስችል ኃይል አልነበራቸውም። የባላባቱ መደብ የነበረውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስታተስ ላለማጣት ሲል በተለይም የመንግስት መኪናዎችን ይቆጣጠርና ተፅዕኖም ያደርግ ነበር። በመሆኑም የሊበራል አስተሳሰብን ለማስፋፋትና ግለሰብአዊ ነፃነትንና ድርጊትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ አይቻልም ነበር። የጊዜው አንገብጋቤ ጥያቄና ተቀዳሚው ተግባርም ዲስፖቲያዊ አገዛዝን መዋጋትንና የሪፓብሊካንን አስተሳሰብ ማስፋፋትና ግለሰብአዊ ነፃነትን ማወጅ ነበር። ተግባራዊ እየሆነ በመጣው ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት ቀስ በቀስ የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣው የከበርቴ መደብና በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ የግዴታ ለከበርቴው መደብ የበላይነት፣ ብሎም ለካፒታሊዝም አይሎ መውጣት አመቺ ሁኔታ ይፈጣራል። በዚህ መልክ ሁኔታዎች በአመቹበት አገር የከበርቴው መደብ የበላይነቱን በመቀዳጀት ለኢንዱስትሪ አብዮትና ብሎም ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ዐይነቱ መንግስትም ቀስ በቀስ ወደ ዘመናዊ ቢሮክራሲያኢ አወቃቀር ያመራና ሙሉ በሙሉ በማደግ ላይ ያለውን የከበርቴ ጥቅም የሚያስጠብቅና የሚያንፀባርቅ ነበር። ስለሆነም መንግስት የሚባለው አወቃቀርና የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠረው ፓርቲ ወይም የህብረተሰብ ክፍል በየአገሩ ውስጥ የጠቅላላውን ህዝብ መብትና ጥቅም በእኩልነት ደረጃ ሊያስጠብቁ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር አልቻለም። የኢኮኖሚ የበላይነትን ያገኘው የከበርቴው መደብና የሱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ምሁራን እንደ አሸን በመፍለቃቸው የከበርቴው መደብ የበላይነትና የካፒታሊዝምን ስልተ-ምርት የሚጠበቅበት ሁኔታ ከሚሊታሪ እስከፖሊስና እንዲሁም እስከ ፀጥታ ጠባቂው ድረስ መደራጀት ቻሉ። የህግ የበላይነትም የሚባለው ነገር ይህንን ሁኔታ የሚያስጠብቅና የሚከላከል እንዲሆን በመዘጋጀቱ፣ በተለይም የሀብትን ሁኔታ አስመልክቶ የህግ የበላይነት የሚለው አስተሳሰብ ይህንን የከበርቴውን መደብ የሀብት ይዞታና የባለቤትነት መብት የሚከላከል ሆኖ ለመዘጋጀት በቃ። በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪ አብዮትና በካፒታሊዝም ዕድገት የተነሳ አብዛኛው ህዝብ ቀስ በቀስ የስራ ዕድል የማግኘት ኃይሉ ከፍ እያለ ቢመጣም የካፒታሊዝም ማደግ በህብረተሰብ ውስጥ የሚደረገውን የሀብት ክፍፍል እያዛባው ሊመጣ ቻለ። በተለይም ወዛደሩ በሳምንት ውስጥ ከአርባ አምስት ሰዓትና ከዚያ በላይ ይሰራ ስለነበር የስራ ሰዓት ቅነሳና የማህበራዊ ጥያቄዎች(Social Question) የመታገያ አጀንዳዎች ሆነው ብቅ በማለታቸው እየተደራጀ በመጣው የወዛደር መደብና ኢንዱስትሪዎችንና ሌሎች ሀብቶችን በሚቆጣጠረው አዲሱ የከበርቴ መደብ መሀከል ፍጥጫና የጦፈ ትግል መካሄድ ተጀመረ። እዚህ ላይ ነው መንግስት የሚባለውና የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች የማህበራዊ ጥያቄዎችን የሚመልሱበትንና የስራ ሰዓት የሚቀነስበትን ሁኔታ በህግ መደንገግ የጀመሩት። ስለሆነም የመንግስት ሚና በህበረተሰብ ውስጥ የሚደረጉ የጥቅም ግጭቶች መረናቸውን እንዳይለቁና ጠቅላላውን ህብረተሰብ እንዳያናጉ አዳዲስ የማሀበራዊና የኢኮኖሚ መሳሪያዎችን በመፍጠር ለካፒታሊዝም ዕድገትና ለአጠቃላይ የሀብት ክምችት መዳበር አመቺ ሁኔታ መፍጠር ችሏል። ካፒታሊዝም ሊያድግና የሀብት ክምችትም ሊዳብር የሚችለው የሰራተኛውና የሰፊው ህዝብ የመግዛት ኃይል ከምርታማነት ጋር እያደገ የመጣ እንደሆን ብቻ በመሆኑ የወዛደሩ መደብ በሙያ ድርጅቱ አማካይነት ከከበርቴው መደብ ጋር የመደራደርና ደሞዝን የማስጨመር ዕድል የማግኘት ኃይሉ ከፍ እያለ ሊመጣ ችሏል። የመንግስቱም መኪናና ፓርቲዎች የነበራቸውን የተወሰነ ነፃነት በመጠቀም ህብረተሰብአዊ ስምምነት እንዲኖር አዳዲስ ህጎችንና ኖርሞችን በማውጣት በአንድ በኩል የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ሲሻሻል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ካፒታሊዝም በማደግና በመስፋፋት የህዝቡን ኑሮ ወሳኝ ለመሆን በቃ። በዚህ መልክ ፊዩዳሊዝምና ኖርሞቹ ቀስ በቀስ በመበጣጠስ በከበርቴው የአሰራር ኖርሞች በመተካት ፈጠራና ስራ፣ እንዲሁም ገንዘብ ማግኘት ህብረተሰብ አዊ ህጎች ለመሆን በቁ።  ካፒታሊዝም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በአሸናፊነት ሲወጣ የመንግስት ዋናው ተግባር በተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አማካይነት የካፒታሊዝምን የሀብት ክምችት በሁሉም አቅጣጫ ማዳበር ሆነ። ይህንን በሚመለከት ኒኮስ ፖላንዛስ የሚባለው ግሪካዊ የማርክሲስት የፖለቲካና የመንግስት ፈላሳፋ በ1970ዎቹ ዓ.ም በፃፈው መጽሀፍ ላይ በሚገባ አስቀምጦታል። በእሱ አባባልና የእሱን ፈለግ ተከትለው ስለካፒታሊስት መንግስታት ተግባር በጻፉት ምሁራን መሰረት የካፒታሊስት መንግስታትና ስልጣንን የሚቆጣጠሩ ፓርቲዎች ዋናው ተግባር ቀድሞውኑ የተነጠፈውን የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ግኑኝነት ማጠናከር ሲሆን፣ ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደየሁኔታው የሚለዋወጥ ነው። ለምሳሌ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማለቂያ ጀምሮ ኢኮኖሚያቸው በጦርነቱ የተከሰከሰ አገሮች ተቀዳሚው የመንግስት ተግባር ኢኮኖሚዎችን እንደገና መልሶ መገንባት(Economic Reconstruction) ነው። ኢኮኖሚው ከሌሎች ጋር  በጥብቅ የተሳሰረ በመሆኑ የአብዛኛዎቹ አገሮች፣ በተለይም የምዕራብ ጀርመን ትላልቅ ከተማዎች እስከሰማንያ በመቶ ድረስ የፈራረሱ ስለነበርና፣ ህዝቡም መጠለያ ስላልነበረው የመንግስት ዋናው ተግባር በመጀመሪያ ደረጃ ለህዝቡ መጠለያ መስጠትና አስፈላጊውን የምግብ ዐይነቶች ለማቅረብ ታግቶ መስራት ነበር። ማንኛውም ሊሰራ የሚችልና የሚፈልግ ሰው የግዴታ መጠለያ፣ ምግብና ማሞቂያ ስለሚያስፈልገው እነዚህን ሁኔታዎች ማሟላት የመንግስት ተቀዳሚውና ዋናው ተግባር ነበር። በዚህም መሰረት ሊሰራ የሚችለውን ሰው ሁሉ በማንቀሳቀስ ከተማዎችን መገንባት፣ መንገዶችንና የባቡር ሃዲዶችን መጠገን፣ ፋብሪካዎችን መልሶ እንዲንቀሳቀሱ ማድረገና ለምርት ክንውን እንዲዘጋጁ ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ በገበያ ኢኮኖሚ ሳይሆን ተግባራዊ የሆኑት በተቀነባበረ የመንግስት ጣልቃ-ገብ ፖሊሲ(State Interventionist Economic Policy) አማካይነት ነው። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአጠቃላይ አነጋገር የኬይኔሲያን የኢኮኖሚክ ፖሊሲ ፍልስፍና ነው እየተባለ የሚጠራው። ኬይንስ የሚባለው የእንግሊዙ ታላቅ ኢኮኖሚስት በተለይም በ1929 ዓ.ም የተከሰተውን ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያቶችን በደንብ ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ ካፒታሊዝም በባህርይው አንድ ጊዜ በዕድገት ሌላ ጊዜ ደግሞ በቀውስና በከፍተኛ የኢኮኖሚ መዛባት የሚገለጽ ስርዓት በመሆኑና፣ ይህም ሁኔታ የግዴታ በየአገሮች ውስጥ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስን፣ እንዲያም ሲል ወደ ግጭት የሚያመራ ሁኔታ ስለሚፈጠር በየጊዜው የሚታየውን የኢኮኖሚ ቀውስ በገበያ ኢኮኖሚ ወይም ደግሞ በረቀቀው የሰው እጅ(Invisible Hand) አማካይነት የሚፈታ ሳይሆን የግዴታ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት እንደሚያስፈልግና፣ መንግስትም ገንዘብ ከባንክ ወይም ከካፒታል ገበያ ላይ በመበደር (Deficit Spending) ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ አለበት፤ በዚህም አማካይነት ብቻ የስራ መስክ በመክፈት ቀውሱን ማብረድ ይቻላል የሚል ነው። በመሰረቱ የኬይንስ ዋና ዓላማ ካፒታሊዝምን ማዳን ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎሊበራል ኢኮኖሚስቶች የሚስተጋባውንና የመንግስትን ጣልቃ-ገብነት የሚቃወመውን ንጽሁ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ(Market Radicalism) ይቃወማል። ስለሆነም ይላል ኬይንስ መንግስት በሚወስደው ጣልቃ-ገብ ፖሊሲ አማካይነት የስራ መስክም ሲከፈት የሰራተኛው የመግዛት ኃይል መጨመሩ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አማካይነት ኢንዱስትሪዎች እየመላለሱ በማምረትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል ለአጠቃላዩ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕምርታ ይሰጡታል። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና አሜሪካንም ጨምሮ የኬይንስን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ለካፒታሊዝም መስፋፋትና መዳበር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረግ ችለዋል። በተለይም የሳይንስ አካዳሚንና የቲክኖሎጂ ምርምር ማዕከሎችን በማቋቋምና በመደጎም፣ የሚፈጠሩትም ቴክኖሎጂዎች በምርት ክንውን ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ በአጠቃላይ ሲታይ ለካፒታሊዝም የሀብት ክምችትና፣ የምርት ዕድገት፣ እንዲሁም ለትላልቅ ኩባንያዎች(Oligopolistic Companies)መስፋፋትና የየአገሩን ኢኮኖሚዎች ከመቆጣጠር አልፈው የዓለምን ኢኮኖሚ እንዲቆጣጠሩ አስቸለዋቸዋል ማለት ይቻላል። በዚህም መሰረት በተለይም ከ1950ዎቹ ዐመታት ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ ዓመታት ድረስ በባንኮችና በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት ሲኖር፣ ትላልቅ ባንኮች የትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ሁኔታ የሚወስኑ ነበሩ። ከ1980ዎች ዓመታት፣ በተለይም ከ1990ዎች ዓመታት ጀምሮ አብዛዎቹ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ከባንክ ጥገኝነት እየተላቀቁ በመምጣታቸው፣ ራሳቸው ወደ አበዳሪነት የተለወጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በተለይም የመኪና ፋብሪካዎችን ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛዎቹ የመኪና አምራች ኢንዱስትሪዎች የየራሳቸው ባንኮች ሲኖራቸው፣ አዲስ መኪና ለመግዛት ለሚፈልግ ሰው ኢንዱስትሪዎች ራሳቸው አበዳሪ በመሆን የመኪናን ምርትና ሺያጭን ማፋጠን ችለዋል። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ሌላ ዐይነት የፋይናንሲንግ ሞዴል በመፍጠር ከባንክ የብድር ጥገኝነት የተላቀቁብትን ሁኔታ መገንዘብ እንችላለን። በሌላ ወግን ደግሞ በተለይም ትላልቅ ባንኮች የአሰራር ስልታቸውን (Business Model) በመለወጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ለላቲን አሜሪካ አገሮች ብድር በማበደር በወለድና በወለድ-ወለድ አማካይነት ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ማዳበር ችለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታና፣ በተለይም ዶላር ከወርቅ ጋር የነበረው የጠበቀ ግኑኝነት መቋረጡና፣ በተለያዩ የካፒታሊስት አገሮች የነበረው የብሬተንስ ውድስ ስምምነት ፈርሶ በምትኩ ተለዋዋጭ(Flexible Exchange Rate System) የሆነ የገንዘብ ልውውጥ ስራ ላይ መዋሉ ባንኮች የአየር በአየር ንግድ እንዲያካሄዱና፣ በተለይም ኢንቬስትሜንት ባንኪንግ በሚባለው ዘርፋቸው አማካይነት በጥሬ-ሀብትና በእህል ላይ ሁሉ የአየር በአየር ንግድ በማካሄድ ከፍተኛ የሀብት ክምችት ማዳበራቸው ብቻ ሳይሆን የብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች ዕድል ወሳኝና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥሬሀብታቸውን በመቆጣጠርና የጥሬ-ሀብት ዋጋ ከፍና ዝቅ እንዲል በማድረግ በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የኢኮኖሚ መዛባት ሊፈጥሩ ችለዋል።
እዚህ ላይ የካፒታሊስት አገሮች እስከ 1970ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ይጠቀሙበት የነበረውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ልቅ በማድረጋቸውና ለካፒታል እንቅስቃሴ የሚያመች ህግ በማውጣታቸው ካፒታሊዝም የበለጠ ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን በማድረግ የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ኢኮኖሚዎች እንዲበዘበዙና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልም  እንዲፈጠርና እንዲጠናከር አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል ማለት ይቻላል። በተለይም ምሁራዊ እንቅሳቃሴ ባልዳበረበትና የመንግስታት ሚና በግልጽ በማይታወቅበትና፣ ካፒታሊዝም በግልጽ መልክ ባላደገበት በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የመንግስታት ሚና ወደ ዘራፊነትና ወደ ጨቋኝነት እንዲያደላ በማድረግ የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታት የግሎባል ካፒታሊዝም የአገዛዝ ሂራርኪ ተቀጥያ በመሆን ወደ ውስጥ ሀብት እየወጣ ወደ ውጭ የሚተላለፍበት ሁኔታ ለመፍጠር ቻሉ። በዚያውም መጠንም ወደ ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣና ህብረተሰብአዊ ኖርሞችን የሚቀናቀኑ ስራዎች እንዲስፋፉ በማድረግ በተለይም ደካማው የህብረተሰብ ክፍልና ሴቶች፣ እንዲሁም የኧረጁ ሰዎች እየፈሩ የሚኖሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። በተለይም የዚህ ዐይነቱ ያለተስተካከለ ዕድገትና የዘረፋ ኢኮኖሚ ስለባ ለመሆን የበቁት ትናንሽ ልጆችና በማደግ ላይ ያሉ ጎረምሳ ልጆች ናቸው። ይህም የሚያሳየው በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በየጊዜው የሚከሰተው አዳዲስ የአሰራር ሁኔታና ኢኮኖሚ ፖሊስ ለውጥና ቀውስ ዓለም አቀፋዊ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውና የአብዛኛዎችን የሶስተኛውን ዓለም አገር ህዝቦች የመኖርና ያለመኖር ሁኔታ እንደሚወስን ነው። በተለይም ዓለም አቀፋዊ የሚባሉት ኢንስቲቱሽኖች፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF)፣ የዓለም ባንክና(World Bank) በሪጂናል ደረጃ የተደራጀው የአውሮፓው አንድነትና(EU) እንዲሁም እንደ ዓለም ንግድ ድርጅት (WTO)የመሳሰሉት የካፒታሊስት አገሮች ኢንስቲቱሽኖች በሶስተኛው ዓለም አገሮች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተፅዕኖ በማድረግ የብዙ ሚሊያርድን ህዝብ ዕድል መወሰንና ሀብታቸው እንዲበዘበዝና ድህነትና ዱርየነት እንዲስፋፋ የማይናቅ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ችለዋል፤ እያደረጉም ነው።

የካፒታሊስት አገሮችን መንግስታት አወቃቀር ስንመለከት ባላፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት ክህግ አወጭው ይልቅ የስራ አስፈጻሚው(Excutive Organ) የየአገሩን ዕድል የሚወስንበትና በዓለም አቀፍ ደረጃም በሰላምና በጦርነት መሀከል ያሉ አማራጭ ሁኔታዎችን ወሳኝ ለመሆን በቅቷል። በተለይም አሁን በተፈጠረው በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ ኃያላን መንግስታት ብቅ ማለትና ተወዳዳሪ መሆን የሚሊታሪውንና የስለላ ድርጅትን ሁኔታ የበለጠ እንዲያጠነክር አድርጎታል። በዚህም የተነሳ ተጨማሪ ባጀት ለሚሊታሪውና ለስለላ ድርጅቱ እየተጨመረ በመምጣቱ ይህ ሁኔታ ሰላምን የሚያሰፍን ሳይሆን የበለጠ ፍጥጫን እያስክተለ በመምጣት ላይ ነው። በተለይም በራሺያ መጠናከር የተደናገጡ አገሮች፣ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ኢኮኖሚያቸውን የበለጠ ሚሊታራይዝ በማድረግ ወደ ቀጥተኛ ግጭት የሚያመሩበትን ሁኔታ እያመቻቹ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል። ሰሞኑን የጸታን ጉዳይ አስመልክቶ እዚህ ጀርመን አገር፣ ሙኒክ የሚባል ከተማ ሃምሳ አገሮች በተካፈሉበት ስብሰባ(Security Conference) ላይ ከዋና አዘጋጁና ከተካፋዮቹም የተሰነዘረው አስተሳሰብ የዓለም ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንደወጣና፣ ብዙ ቦታዎችም የርስ በርስና የጣልቃ-መግባት ጦርነቶች እንደሚካሄድባቸው ነው። ይሁንና ከምኒስተሮችና ከጦር ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ጦርነትና መሳራያ ልቅ በሆነ መልክ ስለመመረቱና ስለመሰራጨቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ አንዳችም ሀተታና ጥናት የቀረበ ነገር የለም። በዓለም አቀፍ ደረጃም ስለሚካሄደው ጦርነትና የርስ በርስ ግጭጥ ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ተብራርቶ አልቀረበም። ከተሳታፊዎቹ ምኒስተሮች የሚሰማው አስተሳሰብ እነሱ ከደሙ ንጹህ እንደሆኑና፣ እነሱ የሚሉትን እንታዘዝም ብለው የራሳቸውን አገር ለማጠንከር የሚታገሉ አገሮችን እንደ ጦር ቀስቃሽ አድርጎ ለማቅረብ ነበር ዋናው ሙከራው። በእኔ እምነት ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተስፋፋው የጦር መሳሪያና ጦርነት ዋናው ተጠያቂዎች የካፒታሊስት አገሮች መንግስታትና ከነሱ ጋር የተሳሰረው የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ ነው። የነዚህም ዋና ዓላማ ዓለምን በጦርነት ማመስ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውዥንብር በመፍጠርና የርስ በርስ ጦርነት ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ በየአገሩ ያለው ህዝብ ሃሳቡን ሰብሰብ አድርጎ ለዕድገትና ለስልጣኔ እንዳይነሳ ማድረግ ነው። ከዚህ ስንነሳ የካፒታሊስት መንግስታ ክላሲካል ከሆነው ወደ ውስጥ የኢኮኖሚ ግንባታ በመላቀቅ- በአብዛኛዎቹ አገሮች ሁሉም ነገር ተስተካክሏል፤ የሚያስፈልገው እነሱን በየጊዜው ማደስና ከሁኔታው ጋር እንዲስማማ አድርጎ ማሻሻል ነው- ወደ ጦርነት ውስጥ በመዝፈቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድብቅና ይፋ የሆነ ጦርነት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ያም ሆነ ይህ መንግስት የሚባለው ትልቅ ኢንስቲቱሽኖችና ስልጣንን የያዙ ፓርቲዎች በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸውና ያላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ዘመን ጣልቃ የሚገቡበት መስክ ውስን እየሆነ ሊመጣ ችሏል። በተለይም ማዕከላዊ ባንኮች ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ በሚያፈሱት ርካሽ ገንዘብ አማካይነትበ ዜሮ ወለድ የሚሰጥ ብድር – የተነሳ ተጠቃሚዎች ከባንክ ጋር ግኑኝነት ያላቸው የተወሰኑ ኢንቬስተሮችና የአየር በአየር ንግድ የሚያካሂዱ ቁማር ተጫዋቾች በመሆናቸው በተለይም በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ መሬትንና ቤቶችን በመቆጣጠር ሰፊውን ሰራተኛ ህዝብ በኑሮ እያማረሩት ነው። ከዚህም በላይ ከቻይና፣ ከራሺያ፣ ከካታርና ከሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ሀብታሞች በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ ቤቶችን በመግዛት ለኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ለመሆን በቅተዋል። የፋይናንስ ካፒታሊዝም ከምርት ክንውን እየተላቀቀ በመምጣቱና፣ ባንኮችም በቀድሞው ሚናቸው ወደፊት ሊገፉና ትርፍ ለማካበት ባለማቻላቸው በኢኮኖሚው ውስጥ ብዙ ገንዘብ በመፍሰሱ የተነሳና በደሃና በሀብታም መሀከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው በመምጣቱ የካፒታሊስት መንግስታትና የመንግስታትን መኪና የሚቆጣጠሩ ፓርቲዎች ይህንን  መረን እየለቀቀ የመጣ የገንዘብ ፍሰትና በተወሰኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች እጅ ሀብት መከማቸት ሊቆጣጠሩ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። ስለሆነም ካፒታሊዝም በጣም እየተወሳሰበ በመምጣቱ ሙሉ በሙሉ እንኳ ባይሆን በአማዛኝ ጎኑ ከመንግስታት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተፅዖኖ በመላቀቅ፣ በአንፃሩ በተለያየ መልክ የሚገለጸው የካፒታሊዝም ስልተምርትና የገንዘብ ክንዋኔ በመንግስታት ላይ ተፅዖኖ የሚያደርጉ ሊሆኑ ችለዋል። በተለይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢንስቲቱሽናላይዝድ በሆነበት ዘመንና፣ ይህንን ፖሊሲ ብዙ አገሮችም ተግባራዊ በማድረጋቸው ምክንያት የተነሳ አንድ መንግስት የአንድን አገር ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ የሚጫወተው ሚና እንዲወላከፍ በማድረግ፣ በተለይም በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ መዛባቱ ብቻ ሳይሆን፣ በተሳሳተ የሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት በየአገሮች ውስጥ ጨቋኝና ዘራፊ መንግስታት ብቅ እንዲሉና እንዲደልቡ በማድረግ ያልተስተካከለ ዕድገት በማስፋፋት ሀብት በከፍተኛ ደረጃ የሚወድምበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በዚህም የተነሳ የቴክኖሎጂ ምጥቅት በማይታይባቸው አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ የማህበራዊ፣ የአካባቢ፣ የፖለቲካና የስነ-ልቦና ቀውሶች በመፈጠር አብዛኛዎቹ አገሮችና አገዛዞች ወዴት እንደሚጓዙ ሊያውቁ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ካፒታሊዝም ልቅ በሆነ መልክ በየአገሮች ውስጥ መስፋፋቱና፣ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታትም በደካማ አገሮች ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረጋቸው ነው። ይህንን ሁኔታ ደግሞ በምሁር መሳሪያ ለመቆጣጠርና መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል ኃይል መዳበር ባለመቻሉና ግልጽ የሆነ ክርክርም ስለማይካሄድ የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና የአገራችንም ዕድል በግሎባል ካፒታሊዝም የሚወሰን ሊሆን በቅቷል። ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች አምባገነናዊ ወይም ፋሺሽታዊ አገዛዞች መጠናከርና ወደ ውስጥ ነፃነትን አፍኖ ጠንካራ ኢንስቲቱሽን ገንብቶ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት አለመቻልና፣ ለሰፊው ህዝብ የስራ ዕድል መክፈት አለመቻል በቀጥታ ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ ስንነሳ የመንግስት መኪና ጨቋኝ መሆንና ሀብት አውዳሚ ኃይል ሆኖ ህብረተሰብአዊ እሴቶችን በመበጣጠስ አንድን ህዝብ አቅመ-ቢስ ማድረግ እንደ ተፈጥሮአዊና እንደ ታሪካዊ ግዴታ ሆነው በመታየታቸው፣ በየጊዜው ምርጫ ተካሂዶ ሌላ ኃይል ስልጣንን ቢቆጣጠርም እንኳ በጨቋኝነቱና ሀብት በመዝረፍና በማባከኑ ወደፊት የሚገፋ እንጂ ሁኔታውን በመቀልበስ መንግስትን ለአገር ግንባታና ለተስተካከለ ዕድገት የሚያዘጋጅበት ሁኔታ ሲፈጠር በፍጹም አይታይም። ባላፉት ስለሳ ዐመታት በብዙ የላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካን አገሮች ምርጫ ቢካሄድም መሰረታዊ የሆነ የመንግስት መኪና አወቃቀር ባለመለወጡ አገዛዞችና መንግስታት የበለጠ ጨቋኝና ህዝብን አቅመ-ቢስ አድርጎ ኑሮውን ለማጨለም በቅተዋል።

ይህ ዐይነቱ አዝማሚያ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮችም እየታየና እያደገ የመጣ ነው። አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት መንግስታት በሚከተሉት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ የተነሳና፣ በተለይም የከበርቴውን መደብ ለማጠንከር ተብሎ የሚወሰዱት የረቀቁ ፖሊሲዎችና የአብዛኛው ህዝብም አስተሳሰብ በኢኮኖሚ ክንዋኔና ገንዘብ በማግኘት ላይ እያተኮረ በመምጣቱ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ይደረጉ የነበሩ ሰፋ ያሉ ትችታዊ ክርክሮች እየቀነሱ መጥተዋል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታና የሰውም አስተሳሰብ ወደ አንድ አቅጣጫ ማድላት ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደምሮ ለፋሺሽትና ለቀኝ ፓርቲዎችና እንቅስቃሴዎች መስፋፋትና መጠናከር አመቺ ሁኔታን እየፈጠረ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከአፍሪካና ከተለያዩ የአረብ አገሮች፣ እንዲሁም ከአፍጋኒስታን በመምጣታቸው ይህንን የሰው ፍሰት የሚቃወሙ ፓርቲዎች በመጠናከር የፖለቲካ አየሩን ሊመርዙና አቅጣጫውም እንዲቀየር ለማድረግ ችለዋል፡፤፡ በዚህም የተነሳ እንደሶሻል ዲሞክራቲክና እንደ ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ የመሳሰሉ በመደናገጥ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ተጋብተዋል።
በተለይም ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ አስተሳሰብ በአሜሪካን እየጠነከረ የመጣ ይመስላል። ፕሬዚደንት ትረምፕ ከተመረጡ ጀምሮ የነጭ የበላይነትን(White Supremacy) መንገስ አለበት የሚለው አስተሳሰብ በመስፋፋቱ የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በጥቁሩ የአሜሪካን ህዝብና በቀኙ የነጭ ህዝብ መሀከል ከፍተኛ ግጭት እየተፈጠረ ነው። ፕሬዚደንት ትረምፕም የመንግስቱን መኪና የበለጠ ጨቋኝ የሚያደርጉ የሚሊታሪና የዎል ስትሪት ሰዎችን በማካተታቸው የነጩ የበላይነት እየተጠናከረና ስር እየሰደደ በመምጣት ላይ ይገኛል። ሰሞኑን በቀረጥ ፖሊሲ አማካይነት ሀብታሙን ለመጥቀም በፓርላሜንትና በሴናት የጸደቀው ፖሊሲ ይህንን የቀኝ አዝማሚያና የመንግስቱን ጨቋኝነት ሲያጠናክር፣ በዚያው መጠንም በደሃና በሀብታም መሀከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው ይመጣል;፡ ይህ በራሱ የታቀደ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ቀውሶች እንዲፋፋሙ በማድረግ፣ ይህንን ለመቆጣጠር ሲል መንግስት የበለጠ የመንግስቱን የስለላና የመጨቆኛ መሳሪያ በማጠናከር በተለይም ስርዓቱን ይቀናቀናሉ በሚላቸው ክሪቲካል አስተሳሰብ ባለቻው ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመነሳት ወደ ረቀቀ ጨቋኝነት እንዲያመራ ይገደዳል ማለት ነው።  ለማንኛውም መንግስት ስለሚባለው ነገር ከሶክራተስና ፕላቶ ጀምሮ፣ ከዚያም በኋላ በማዕከለኛው ዘመን በነበሩ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች ድረስ ሰፊ ጥናትትና ምርምር በመካሄድ አንድ ስምምነት ላይት ተደርሷል። ይኸውም መንግስት የሚባለውን መኪናን ሰዎች የሚቆጣጠሩት በመሆኑ፣ እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ስነ-ምግባርና ግብረ-ገብነት  ያላቸው መሆን ሲገባቸው፣ አንድን ህብረተሰብ ለማስተዳደር ይችሉ ዘንድ የሚመሩበት አንዳች በሳይንስና በፍልስፍና የተመረኮዘና የተፈተነ ዕውቀት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል የሚል ነው። በዚህም መሰረት በተለይም ጀርመንን ወደ ስልጣኔ እንድታመራ ካደረጉት ታላቅ ሳይንቲስቶች ውስጥ አንዱ፣ ቪልሄልም ሁምቦልድት በሚባለው ዕምነት መሰረት የአንድ መንግስት ዋና ተግባር ለአንድ ህዝብ ከፍተኛውን ነፃነት እንዲያገኝ ማድረግና ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ጥበብ የተሞላበት ፖለቲካ ማካሄድ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ የመንግስት መኪና ውስጥ ዱርዬዎች፣ ዘራፊዎች፣ ሰላዮችና ህብረተሰብአዊና ታሪካዊ ኃላፊነት የማይሰማቸው ስልጣንን የመቆናጠጥ መብት የላቸውም። ስለሆነም በአንድ የመንግስት መኪና ውስጥ የሚካተቱ ኃይሎች ከፍተኛ የሞራል ብቃትነት ያላቸውና፣ በምንም ዐይነት የአገራቸውን ጥቅም ለሌላ የውጭ ኃይል አሳልፈው የማይሰጡና፣ አገራቸውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ እንዲሁም የጥበብ ባለቤት ለማድረግ ቀን ከሌት ሳይሰለቹ የሚሰሩ ዕንቁ ባህርይ ያላቸው ሰዎች መሆን አለባቸው። የአንድ መንግስትም ተግባር በዚህ ዐይነቱ መሰረተ-ሃሳብ በመመራት በአገሩ ውስጥ የተሰተካከለ ዕድገት እንዲመጣ ሁለ-ገብ(Holistic Economic Model) የሆነ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡን ማጎልበስና አገሩን ማጠንከር ነው። ስለሆነም መንግስት የሚባለው ፍጡር በተለይም ንቁ የሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዕውቀት፣ በምክርና በርካሽ ብድር ድጋፍና ዕርዳታ በመስጠት ኢኮኖሚው በመሰረቱ በንግድ ላይ ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ እንዲካሄድ በማድረግ የአንድን አገር ኢኮኖሚ መሰረት ማጠንከር ነው። ይህም ማለት የመንግስት ሚና ወደ ጨቋኝነትና ወደ ዘራፊነት የሚቀነስ ሳይሆን ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም አጠቃላይ የሆነ ህብረተሰብአዊ ሀብት(Social Wealth) የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ስልጣንን የተቆናጠጡ የህብረተሰብ ኃይሎች የአንድን አገር ሀብት እንደፈለጉ ለወጭ ኩባንያዎች የሚቸበችቡና አካባቢ ወድሞ ማህበረሰብአዊ ቀውስ እንዲከሰት የሚያደርጉ ሳይሆን፣ አንድ አገርና ህዝብ የሚበለጽግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
ባጭሩ የአንድ መንግስትና አገዛዝ ዋና ተግባር የአንድን ህዝብ የማምረት ኃይል ማሳደግና ማስፋት ነው። ይህንን ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫ እርስ በርሱ ሊያያዝ የሚችል የስራ-ክፍፍል(Division of Labour) እንዲዳብርና እንዲስፋፋ አስፈላጊውን እርምጃዎች መውሰድና፣ አንዳንዶችንም ኢንስቲቱሺናላይዝ ማድረግ ነው። ለስራ-ክፍፍል መዳበር ደግሞ የግዴታ የቴክኖሎጂ ወይም የማኑፋክቱር አብዮት መካሄድ አለበት። ልዩ ልዩ ምርቶች ሊመረቱና በእንዲስቱሪዎችና በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፎች መሀከል የንግድ ልውውጥ ሊካሄድና የገንዝብም የመግዛት ኃይል ሊጠናከር የሚችለው በማኑፋክቱር አማካይነት ብቻ ነው። ለማኑፋክቱር ወይም ደግሞ ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መደባር የግዴታ የማሺን ኢንዱስትሪ ቁልፍ ቦታን ሲይዝ፣ ይህ መስክ የግዴታ ከሳይንስ ምርምር ጋር መያያዝ አለበት። በዚህ አማካይነት ብቻ አንድ አገር ለጊዜው ጠቀሜታ ላይ የሚውልና ለረጅም ጊዜም የሚያገለግሉና አንድን አገር ከአደጋ የሚከላከሉ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን ማምረት ትችላለች። ባጭሩ ካለሳይንስና ተከታታይነት ካለው የቴክኖሎጂ ዕድገት ውጭ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም ሊታሰብ አይችልም። የአንድንም ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል አይቻልም። አንድ አገር ልትጠነክርና ልትከበርም የምትችለው በሳይንስና በቴክሎኖጂ አማካይነት በሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገትና የንግድ እንቅስቃሴ አማካይነት ብቻ ነው።

እስከዛሬ ድረስ በአገራችን ውስጥ እንደሌሎች ህብረተሰብን የሚመለከቱ ነገሮች የተሰራው ትልቁ የታሪክ ወንጀል መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? በአንድስ አገር ሰላምና ብልጽግና እንዲመጣ ከተፈለገ የአንድ አገዛዝ ፍልስፍናና መንግስታዊ አደረጃጀት ምን መምሰል አለበት? ለመሆኑ መንግስት የሚባለው ፍጡር አንዳች ርዕይ ሊኖረው ይገበዋል ወይ? ወይስ በዘፈቀደ እንዳሻው እየተነሳ ይህንን ወይንም ያንን አገርን የማይጠቅም፣ ህዝብን የማይሰበስብና ታሪካዊ ስራን የማያሰራ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ በጭፍኑ የሚሸጋገር ኃይል ነው ወይ ? በተለይም ቀደም ብሎም ሆነ በተማሪው እንቅስቃሴ ዘመንና፣ ከዚያም በኋላ በዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ጥያቄ ላይ ውይይት፣ ጥናትና ከርክር ለማድረግ ባለመቻሉና፣ ወይም ደግሞ በዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ መወያየት እንደ ኃጢአት ወይም እንደ ወንጀል ተደርጎ በመወሰዱ በተለያየ ጊዜ ስልጣንን በአጋጣሚ የሚጨብጡ ኃይሎች የአገራችንና የህዝባችንን ዕድል በማጣመምና በማበላሸት ሰፊው ህዝብ እንደሰው ሆኖ እንዳይኖር ለማድረግ በቅተዋል። ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ስልጣናቸውን በውጭ ኃይሎች ድጋፍ ካጠናከሩ በኋላ እነሱ ብቻ የመኖር መብት ያላቸው ይመስል የህዝብን ሀብት በመቆጣጠርና ህዝቡን ራሱን በመግፋትና ለማኝ እንዲሆን በማድረግ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ አለው የሚባለው ህዝብና፣ የሰው ልጅም የተፈጠረበት አገር ነው ተብሎ የሚታመንበት አገር በድህነት፣ በረሃብ፣ በጦርነት፣ በስደትና በበሽታ እድሜ ልኩን እየተሰቃየ እንዲኖር ለማድረግ በቅተዋል።  የአገራችን መጥፎ ዕድል ሆኖ እኛ ከተፈጠርን ጀምሮ አገራችንና ህዝባችን እንደዚህ ዐይነቱ በእነፕላቶንም ሆነ በእነ ሁምቦልድት የተስፋፋው የአንድን መንግስት ምንነትና ተግባር የሚመለከት መሰረተ-ሃሳብ ባለመስፋፋቱና እንደመመሪያም ሆኖ ባለመወሰዱ በአማዛኝ ጎኑ አገራችን የአንድ አገር ምንንት፣ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው ? ታሪክስ እንዴት ነው ሊሰራ የሚችለው? ብለው በሚያወጡና በሚያወርዱ ሰዎች ወይም አገዛዞች ለመመራት ወይም

ለመተዳደር ዕድል ባለማግኘቷ ዛሬ የምናየው አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመውደቅ ተገደናል። ከአፄ ኃይለሰላሴ ጀምሮ በአገራችን ምድር የተስፋፋና በውጭ ኃይሎች የተቀነባበረና፣ ከህዝብ ፍላጎትና ዕድገት ጋር የማይጣጣም፣ የህዝብን ሀብት የሚመጥ ቢሮክራሲያዊ የመንግስትና የፀጥታ ኃይል- በመሰረቱ ረባሽ ኃይልና፣ አንድ ህዝብ በፍርሃት ተውጦ እንዲቀር የሚያደርግ ከካፒታሊስት አገሮች የተወሰደ የመንግስት አገነባብ ፈሊጥ- በመስፋፋቱ ዋናው የመንግስት ተግባር አንድን አገር ወደ መገንባትና ማጠንከር፣ እንዲሁም ብሄራዊ ሀብት እንዲፈጥር ማድረግ ሳይሆን ወደ ጨቋኝነት እንዲቀነስ በማድረግ ህዝብ እየፈራና የመፍጠር ችሎታው እንዳይዳብር በማድረግ ደቅቆ እንዲቀር የሚያደርግ ሆነ። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ በአንዳች ፍልስፍናና ዕውቀት ላይ ያልተገነባ መንግስታዊ አወቃቀር በተለያየ ጊዜ በሚፈጠር ቀውስ የተነሳ የሰላዮችና የአላጋጮች፣ እንዲሁም የተንኮል ሸራቢዎች መሰግሰጊያ በመሆን አገዛዙ አንዳለ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ጠቅላላው ህብረተሰብ የሚናጋበት፣ ሰላም የሚደፈርስበትና ህዝቡም በፍርሃት ተውጦ የሚኖርበት ሁኔታ ተፈጠረ። በተለይም በአብዮት ወቅት የተከሰተው የተደናበረና የርዕዮተ-ዓለም ግልጽነት የሌለበት የትግል ሁኔታ የመንግስቱን መኪና የሰላዮች፣ የአድርባዮችና የተንኮል ሸራቢዎች መሰግሰጊያ በማድረግ ሁሉም የሚፈራራበት ዘመን ለመሆን ቻለ። „ ስልጣን እስከያዙ ድረስ ነው መዝረፍና መበልጸግ “ በሚለው የሃበሾች አጉል ፈሊጥ በመመራትና በህዝብና በአገር ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አንዳችም ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባት በአገራችን ምድር ውስጥ ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል ሊሰራ በቃ።
በተለይም ህብረተሰብአዊ ለውጥና መሻሻል ከኮሙኒስታዊ አስተሳሰብ ጋር የሚስተካከል አስተሳሰብ መስሎ ለታያቸው የሲቪልና የፀጥታው፣ እንዲሁም የተወሰነው የሚሊታሪ ቢሮክራሲ ክንፍ በአብዮቱ ጊዜ የተወሰዱትን እርምጃዎች በሙሉ ለመቀልበስ ሲሉ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በማበርና ድጋፍ በማግኘት፣ እንዲሁም የፀረ-ኩሙኒዝም ሊግ የሚባል ድርጅት በማቋቋምና የተደናበሩ ኃይሎችን በመሰብሰብ በአገሪቱ ላይ አጠቃላይ ጦርነት በማወጅ አገራችን እንድትበታተንና የዛሬው የወያኔ አገዛዝ እጅ ስር እንድትወድቅ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ቻሉ። ይህ ታሪክን ለመገንዘብ አለመቻል፣ ማንኛውም ህብረተሰብ በየጊዜው ጥገናዊ ለውጥና መሻሻል እንደሚያስፈልገው ባለመረዳት የተወሰደ ከአገር ወዳድነት ስሜትና ዕውቀት ማነስ የተነሳ አገርን የሚያፈራርስ እርምጃ በማንኛውም አገር ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። ከአንድ የሰላም፣ የብልጽግናና የዕድገት እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጠር ከሆነ ኃያል መንግስት ጋር በማበርና ከሱ ድጋፍ በማግኘት በአንድ አገር፣ በህዝቦቿና በታሪኳ ላይ ዘመቻ ማድረግ ኢትዮጵያኖችን የሚወዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ ሌላ አገርና ህዝብ ያለ አይመስለኝም።

በአንፃሩ ግን አደጉ የሚባሉ የካፒታሊስት አገሮችንና የስካንዲኔቪያን አገሮችን የመንግስት አወቃቀርና የአገር አገነባብ ታሪክ ገርደፍ ገርደፍ አድርገን በምናይበት ጊዜ፣ እነሱም እንደኛው ዐይነት የመንግስት አገነባብ ቢኖራቸውና ፣ የመንግስቱም መኪና በሰላዮች፣ በአፈንጋጮችና በተንኮለኞች ቢሰገሰግ ኖሮ እንደዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ባልቻሉና ውስጣዊ መረጋጋትም ባልታየባቸው ነበር። በእኛና በእነሱ መሀከል ያለውን የመንፈስ ልዩነት ስመለከት የእኛ ኢትዮጵያውያን ጭንቅላትና አስተሳሰብ ለታላቅ ስራ ያልተዘጋጀ መሆኑን ነው ማረጋገጥ የሚቻለው። ስለሆነም የካፒታሊስት አገሮችን የመንግስት መኪና አወቃቀር ጠጋ ብለን በምንመለከትበት ጊዜ አጠቃላዩ ህብረተሰብአዊ ዕድገትና የመንግስት አወቃቀር አንድ ላይ ተያይዘው ነው የሚሄዱት የሚመስለው። ይህም የሚያረጋግጠው በተለያየ ጊዜ በካፒታሊዝም የዕድገት ደረጃ ውስጥ ስልጣንን የሚይዙ ኃይሎች የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ መሰረት ለማስፋትና ለማጠንከር የሚወስዷቸው በቲዎሪ የተፈተኑ ፖሊሲዎች እንዳሏቸው ነው። ይህ ዐይነቱ ልምድ መኖርና በተለያዩ ምሁራን ዘንድ የጦፈ ክርክር ለመካሄድ በመቻሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚለው መሰረተ- ሃሳብ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ውጭ ሊታሰብ የማይችልና፣ ባማሩ ከተማዎችና በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች በተያያዙ የሚገለጽ መሆኑን ነው ግንዛቤ ውስጥ የተገባው። ካፒታሊዝም በአገር ውስጥ ሊስፋፋና አንድን ህብረተሰብ ሊያቅፍ የሚችለው ከላይ የተጠቀሱት መሰረተ-ሃሳቦች ሲሟሉ ብቻ ነው። በአንድ አገር ውስጥ ያልተሰተካከለ ዕድገት ካለ ለካፒታልና ለሌሎች የሀብትና የስራ-ጉልበት እንቅስቃሴ እንቅፋት ስለሚሆን በዚያው መጠንም በውድድር ላይ የተመሰረተ ካፒታሊዝምና ሰፋ ያለ የሀብት ክምችት እንዳይዳብርና እንዳይስፋፋ ያደርጋል። ይህ በራሱ ደግሞ የሰው ኃይል ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ አንዳንድ ከተማዎች በሰው ብዛት እንዲጨናነቁና ሪሶርስም እንዲወድም ያደርጋል። ስለሆነም በተለይም ወደ አገራችን ስንመጣ ዕድገት የሚባለው ፈሊጥ ከቡናና ከሻይ፣ ከጨአትና ከአበባ ተከላ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ይህ ዐይነት ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በንግድ ልውውጥ ሊገለጽ የሚችልና፣ ብዙ ቫሉታ በማግኘትና ባለማግኘት የሚተነተን ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር ስለኢኮኖሚ ዕድገት ያለን አስተሳሰብ የህብረተሰብን ዕድገትና ታሪክን፣ እንዲሁም የውስጥ ገበያን አገነባብ የሚፃረር፣ ለሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚ የሚያመችና፣ ማጭበርበርን እንደ አንድ የንግድ ፈሊጥ አድርጎ የወሰደ አካሄድ ነው ሊስፋፋ የቻለው ማለት ይቻላል። ይህ ደግሞ የግዴታ ተበላሽቶና ተወላግዶ በምንም ዐይነት ቲዎሪና ሳይንስ ሳይመረኮዝ በዘፈቀደ ከተገነባው ወደ ተራ ጨቋኝነት ከተለወጠው መንግስታዊ መኪና ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ጠቅላላው የአገራችን የተዝረከረከ ሁኔታ የዚህ ዐይነቱ ፍልስፍና አልባ የሆነ የመንግስት መኪና ነጸብራቅ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ውጭ ማሰብና በዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ  ጥያቄ ላይ ውይይትና ክርክር እንዳይኖር ማድረግ ትልቅ የታሪክ ወንጀል መስራቱ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ህዝብ በሚቀጥሉት ሁለት መቶና አምስት መቶ ዐመታት ታሪክን እንዳይሰራ ተንኮል እንደመሸረብ ይቆጠራል።
ከዚህ ስንነሳ የአንድን መንግስት ምንነትና ተግባር በሚመለከት በኩል በሁላችንም ዘንድ ከፍተኛ የሆነ፣ የሳይንስ፣ የቲዎሪና የተግባር ክፍተት አለ። የመንግስትን ምንነት እስካልተረዳን ድረስና፣ በተለይም ደግሞ የአንድ አገር የመንግስት መኪና የውጭ ኃይሎችን ጥቅም በሚያስጠብቁ ግለሰቦች የሚሰገሰግበትና፣ ዋና ተግባራቸውም ቴክኖሎጂያዊ ለውጥና በዚያ አማካይነት ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣ የሚያግዱ እስከሆነ ድረስ ለለውጥ ዝግጁ አይደለንም ማለት ነው። ከካፒታሊስት አገሮች፣ ከራሺያ፣ ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከሰሜንና ከደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ከሲንጋፖርና ከአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ አገሮች የምናገኘው ልምድና የምንቀስመው ትምህርት የእነዚህ አገሮች መንግስታት በሰላዮችና በአጭበርባሪዎች ቢሰገሰጉ ኖሩ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ባልቻሉ ነበር። እነዚህ መንግስታት የሚያስቸግሯቸውን አንዳንድ ኃይሎች፣ በተለይም ራሺያኖች በራሺያን ዘዴ እየተከታተሉ ባይደመስሱ ኖሮ ራሺያ እንደአገር ልትኖር ባልቻለችም ነበር። ዛሬ የምናየውም በጣም የተወሳሰበ የሚሊተሪ ቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ባልበቃች ነበር። ይህን ሁሉ የማትተው የመደብ ግኑኝነት(Social Relationship) የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ ከቁጥር ውስጥ ሳላስገባ ነው።

ነገሩን መቋጠሪያ ለመስጠት፣ በአንድ አገር ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ስዎች ሲኖሩ፣ የእነዚህ ሰዎች ምኞትና ፍላጎት ሁሉ ሰላም፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ብልጽግና ማግኘት ነው። እያንዳንዱ ሰው በዓለም ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚኖረው። ስለሆነም በተቻለ መጠን ከስቃይ ይልቅ ደስታን መጎናጸፉ የተፈጥሮ ህግ ሆኖ መወሰድ አለበት። ማንኛችንም ስቃይን አንሻም። በእኔ ላይ ስቃይ እንዲደርስ የማልፈገውን ያህል፣ በሌላውም ላይ እንዳይደርስበት ምኞቴ መሆን አለበት። የእኔ በሰላም መኖር ከሌላው በሰላም መኖር ጋር የተያይዘ እንደመሆኑ መጠን፣ የሱ ስቃይ የእኔም፣ የእሱ ደስታ የኔም መሆኑን መገንዘብ ስችል ብቻ ነው ጤናማ ህብረተሰብ መገንባት የሚቻለው። ይህ መሰረተ-ሃሳብ ግን ልዩ ዐይነት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሰፈነበትና፣ ኢትዮጵያዊነትም የረቀቀ አስተሳሰብ ነው ተብሎ በሚወሰድበት አገር የተለመደና እንደመሰረተ-ሃሳብ የተወሰደና ከደም ጋር የተዋሃደ አይደለም። ሁላችንም ስለ ኢትዮጵያዊነት ያለን ስሜት ከህዝቡ የማቴሪያል ዕድገት ጋር የሚያያዝ አይደለም። በሁለ-ገብ ዕድገት የሚገለጽ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ምጥቅት ጋር የተያያዘ አይደለም። ኢትዮጵያዊነትም በአማሩ ከተማዎችና በመንደሮችም የሚገለጽ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊነት የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ፣ የማይታይ፣ የማይበላና የማይቀመስ እጅግ የረቀቀስ አስተሳሰብ ሆኖ ነው የሚሰማን። ስለሆነም ስለ ኢትዮጵያዊነት ያለን ህልም ቅዠት እንጂ በሚታይ ነገርና በመንፈሳዊ ተሃድሶ የሚገለጽ አይደለም። ይህ ዐይነት ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር ያልተያያዘ ትራዲሺናላዊ የሆነ አስተሳሰብ ነው ሁላችንም በግልጽ እንዳንመልከት፣ እንዳንጠይቅና እንዳናስብ ጭንቅላታችንን አንቆ የያዘው። ይህ ዐይነቱ አመለካከታችን ራዲካል በሆነ መልክ እስካልተለወጠ ድረስ፣ እንዲያውም የኢትዮጵያ ሁኔታ እዚያው ተግማምቶና ቀጭጮ እንዲቀር ነው ከፍተኛ አስተዋፅዖ የምናደርገው። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከፈልግን የግዴታ የመንግስትን ሚናና ምንነት እየመላለስን ማንሳትና መተንተን አለብን። መንግስትና የመንግስትን መኪና የሚጨብጡ ሰዎችንም የሞራልና የስነ-ምግባር ብቃትነት እያነሳን መወያየት አለብን። ከዚህም ጋር ተያይዞ በየኢፖኩ የሚፈጠሩት ሁኔታዎች፣ የኃይል አሰላለፍ ለውጦችና የምርት ግኑኝነት መለወጥና የግሎባል ካፒታሊዝም መስፋፋትና የመንግስትን መኪና ለራሱ የሀብት ማካበቻ መሳሪያ ማድረግ፣ በአገራችን ውስጥ በሚፈጠረው ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት ላይ፣ የፍጆታ አጠቃቀም ጉዳይ ላይና፣ የስነ-ልቦና መጠንከርና መላላት ላይ የሚኖረውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት እያነሱ መወያየት ስለመንግስት ምንነትና መሰረታዊ ተግባር ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስችለናል። በዚህም መሰረት ስለብሄራዊ ስሜት መዳበርና፣ የብሄራዊ ስሜት መዳበርስ በምን መልክ ነው የሚገለጸው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳትና ራስን ማስጨነቅ በመንግስት ጥያቄ ዙሪያ ለምናደርገው ውይይት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥርልን ይችላል።

ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ ያለ አገዛዘ ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ሲሆን ጠቅላላው ህዝብ ደስታን የሚጎናጸፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። እኩልንት ማስፈንና የህዝቡ የመፍጠር ችሎታ የሚዳብርበትን አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ህብረተሰቡ ወደ ተወሳሰበና ወደተቀላጠፈ የአኗኗር ዘዴ ሊሸጋግርበት የሚችልበትን ሁኔታ ማዘጋጀት የአንድ መንግስት ታሪካዊ ግዴታና ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በተቃራኒው ግን አንድ አገዛዝ እንደ አገራችን ወደ ተራ ዘራፊነት የሚለወጥ ከሆነና፣ ስራው ሁሉ መረጋጋት እንዳይሆን የሚያደርግ ከሆነ፣ ወደ ተራ አሻጥር ሰሪነት ተለውጦ ህዝቡን በዘለዓለማዊ ውዝግብ እንዲኖር የሚያደርግ ከሆነ የዚህ ዐይነቱ አገዛዝ በኃይል መደምሰስ ታሪካዊ ግዴታ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የአናርኪስቶች ሳይሆን የተቀደሱ ሰዎች ወይም ፈላስፋዎች አመለካከት ነው። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ዕድሜ ልኩን እየተሰቃየ፣ እየተገደለ፣ ቀየው እየወደመና እየተሰደደና እንደህብረተሰብና እንደማህበራዊ ኃይል የመኖር መብት የለወም የሚል የተፈጥሮ ህግ ስለሌለ ነው። አንድ መንግስት ከህዝብ በላይ ሊሆን አይችልም። እንደዚሁም የመንግስትን መኪና የጨበጡ ልዩ ሰዎች አይደሉም። ስለሆነም ከህዝብና ከአገር በላይ ሊሆኑ አይችሉም። „ ንጉሱ ዕርቃኑን ነው “ እንደሚባለው እንደፈላስፋዎች አነጋገር፣ በአንድ የመንግስት መኪና ላይ የተቀመጡ ሰዎች ከሌላው ሰው  የሚለዩበት ምንም ነገር የለም። ሊከበሩና ሊወደሱ የሚችሉት የየአገራቸውን ህገ-መንግስት እስካከበሩና በሱ አማካይነት የህዝብን ጥያቄ መመለስ የቻሉ እንደሆን ብቻ ነው። ጠንካራ አገር ለመገንባት የየአገራቸውን የሰው ኃይልና የጥሬ-ሀብት ማንቀሳቀስ የቻሉ እንደሆነና፣ በየቦታውም ጠንካራና ዲሞክራሲያዊ ኢንስቲቱሽኖችን የሚገነቡ ከሆነ በህዝብ ይከበራሉ፤ በታሪክም ሲወደሱ ይኖራሉ።

የዛሬው አገዛዝ አነሳስና ወደ ፋሺዝምነት የመለወጥ ሂደት !

የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን የህብረተሰብአችን ውጤት ነው። የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አንድ ላይ በመጣመር ለእንደዚህ ዐይነቱ ዘራፊና ፈሺሽታዊ አገዛዝ ስልጣንን መቆናጠጥ አመቺ ሁኔታ ሊፈጥሩ ችለዋል ማለት ይቻላል። የህብረተሰብአችን ውጤት ነው ስል ምን ማለቴ ነው፟ ? አንድስ ህብረተሰብ እንዴት እንደዚህ ዐይነቱን እጅግ አደገኛና ጭንቅላቱ የተዘበራረቀበት ኃይል ሊፈጥር ይችላል ? ይህንን ምናልባት ግልጽ አድርጎ ማተት አያቻልም። እንደዚህ ዐይነት በተንኮልና ሌላውን በማጥፋት ላይ የተገነባ መንግስታዊ አወቃቀርና አገዛዝ በዓለም ታሪክ ውስጥ የታወቀ ወይም የተለመደ ባለመሆኑ በኮምፓራቲቭ ጥናት አማካይነት ከሌሎች አገሮች ጋር በማወዳደር እንደማስረጃ በመውሰድ አጥጋቢ የሆነ ሳይንሳዊ ትንተና መስጠትና አንባቢውን ማሳመን አይቻልም። ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮች በምድር ላይ የሚታይ ተመሳሳይ ችግር ቢኖርባቸውም፣ በህሊና አወቃቀር እንደኛ አገር በተንኮልና በሽወዳ የተካነ የህብረተሰብ ኃይል ያላቸው አይመሰለኝም። ይህ ጉዳይ በተለይም ምሁሩን የሚመለከት ነው። የኛው በጣም ልዩ የሆነና ለሳይኮሎጂስቶችም አስቸጋሪ የሆነ ጭንቅላት ያለን ነው የሚመስለው። ዕምነት የማይጣልበት፣ ግራ አሳይቶ ወደ ቀኝ የሚዘምት፣ የርዕዮተ-ዓለም ግልጽነት የሌለው፣ መንሾካሾክ ዋናው የኑሮ ስልቱ የሆነ፣ በምንም ዐይነት ትልቅ ስራን ለመስራት ያልተዘጋጀና፣ በትንሹ የሚደሰትና፣ ለትንሽ ነገር ብሎ ወንድሙን አሳልፎ የሚሰጥ የህብረተሰብ ኃይል አገራችን ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ላይ እንድትወድቅ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ የማይታበል ሀቅ ነው። የአንድ አገር ዕድገትና ፀረ-ዕድገት ሁኔታ ከመንግስትና ከምሁራዊ ኃይል ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ የአንድ አገር ሁኔታ ከተበላሸ፣ አንድ ኃይል ስልጣንን ነጥቆ ወደ ፋሺዝምነት የሚያመራ ከሆነ፣ ይህ ዐይነቱ ሂደት ህብረተሰብ ውስጥ ከሚከናወነው በብዙ መልኮች ከሚገለጸው ነገር ተነጥሎ ሊታይ የሚችል ጉዳይ አይደለም። ይህ ዐይነቱ ተፈጥሮአዊ ባህርይ ሳይሆን ጭንቅላታችን በዕውነተኛ ዕውቀት ያልተኮተኮተና ያልዳበረ በመሆኑ ብቻ ነው። ስለሆነም አዕምሮአችን አስተዋይነት የጎደለው፣ አንድን ነገር ሎጂካዊ በሆነ መልክ ለማየት የማይችል፣ አንድን ነገር በተወሳሰበ መልክ ተረድቶ መልስ ለመስጠት የማይችልና፣ በተለይም ደግሞ ችግርን በመፍጠር፣ የችግሩ አንድ አካል ለመሆን አለመረዳት፣ ችግርን ፈጣሪ እኔ ሳልሆን ሌሎች ናቸው በማለት ከሀቀኝነት ማፈግፈግ ዋናው ባህርያችን በመሆን ግልጽነትና ሳይንሳዊ ለሆነ ስራ እንዳናመችና እንዳንዘጋጅ ተደርገናል። ከዚህም ባሻገር ስንትና ስንት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን ክብር መስጠትና፣ ወንጀል እንዳልሰሩ እየመላለሱ በመጠየቅ ለተወሳሰበው የአገራችን ችግር ቁልፍ መፍትሄ ያላቸው ይመስል ተደማጭነትን እንዲያገኙና ህዝብን እንዲያሳስቱ ማድረግ እነዚህ ሁሉ የሚያረጋግጡት፣ በአንድ በኩል ስለሰው ልጅ ያለን የሰብአዊነትና የእኩልነት አመለካከት የቱን ያህል የተዛባ መሁኑን ነው፣ በሌላ ወገን ደግሞ አንድን ነገር ሎጂካዊ በሆነ መንገድ ለማሰብ እንደማንችል ነው።

ሰለሆነም ስለዛሬው አገዛዝ ባህርይ በምናወራበት ጊዜ የኛንንም ባህርይና ምንነት፣ የፈጸምናቸውን ወንጀሎች ወደ ጭንቅላታችን ውስጥ ሰርገን በመግባት መመርመር መቻል አለብን። የለም እኛ ከደሙ ንጹህ ነን፣ ወንጀል ሰርተን፣ ሰልለንና አገር አፈራርሰን በቦታው አልነበርንም የምንል ከሆነ ባህርያችን ስድስት ሚሊዮን ይሁዲዎችን በአሰቃቂ መልክ ከጨረሱት የጀርመን ናዚዎች የሚለይበት አንዳችም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ናዚዎችን ናዚዎች የሚያሰኛቸው ከሰባ ዐመት በኋላም ወንጀላቸውን አለማመናቸውና ብቅ የሚለውም አዳዲስ ኃይል እንደዚህ ዐይነት አሰቃቂ ድርጊት መፈጸሙን ባለማመኑ ነው። አንድ ሰው ሀቀኛና የተማረ ነው የሚያሰኘው ስህተት መስራቱን ያመነና ለማረምም ዝግጁ የሆነ እንደሆን ብቻ ነው። ስህተቱንም ወደ ውጭ አውጥቶ በግልጽ የተናገረ እንደሆን ብቻ ነው ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው አንድ ቁም ነገር መጠበቅ የሚቻለው።

ያም ተባለ ይህ አንድ ሰውም ሆነ በቡድን የተደራጀ ኃይል በአንድ አገር ውስጥ በግልጽ የሚታይ የኢኮኖሚ፣ የማህበረሰብ፣ የባህልና የሳይኮሎጂካል ሜክ አፕ ነጸብራቅ ወይም ውጤት ነው። በተለይም ደግሞ አንድ ህብረተሰብ ጭቅንቅላትን የሚያድስ በልዩ በልዩ መልክ የሚገለጽ የዘመናዊነት ሂደት ውስጥ የማለፍ ዕድል ካላገኘ ጭንቅላቱ መዳበር አይችልም ማለት ነው። በፈላስፋዎችና በሳይኮሎጂስቶች ምርምር መሰረት አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ወይም ህብረተሰብ ግንዛቤ ያገኝ ዘንድ ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት መኮትኮት ያለበት ብቻ ሳይሆን የግዴታም ለጭንቅላቱ መዳበር ዕምርታ የሚሰጠው በምድር ላይ የሚታየው የማቴሪያል ሁኔታም መለወጥ አለበት። በተለይም አንድ ህብረተሰብ በስራ ክፍፍል(Division of Labour)፣ በንግድ፣ በከተማዎችና በመንደሮች፣ እንዲሁም ጭንቅላትን ሊያድሱና ሊያዳብሩ በሚችሉ ነገሮች የሚጋፈጥ ካልሆነና፣ ኑሮው እዚያው በዚያው የሚሽከረከር ከሆነ በእንደዚህ ዐይነት ህብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ አንድን ነገር በተወሳሰበ መልክ መረዳትና አርቆ በማሰብ ለአንድ ችግር መልስ ሊሰጥ በፍጹም አይችልም። አንድን ነገር በተወሰነ መነጽር ስለሚመለከት ያ ችግር በአንድ የህብረተሰብ ክፍል ወይም ብሄረሰብ ላይ ስላነጣጠረ ነው ጭቆናና መበደል ሊፈጠር የቻለው በማለት ወደ ተሳሳተ ድምደማ ላይ ይደርሳል። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ ህብረተሰብ ማደግና አለማደግ፣ ከህብረተሰብ የዕድገት ታሪክ አንፃር፣ በየጊዜው ስልጣንን የሚቆናጠጡ ኃይሎች የነበራቸውን ዕውቀትና የሚመሩበትን ፍልስፍና፣ በተለይም ደግሞ ከአገዛዝ ክልል ወጣ ብሎ የሚደረግ ሰፋ ያለ የምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገርና ህብረተሰብ ውስጥ፣ እንዲሁም ፖለቲካ የሚባለው አንድን ህብረተሰብ ማስተዳደሪያ መሳሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ በሌለበት አገር ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ፖለቲካ ነክ ፖሊሲዎች አንድን ብሄረሰብ ለመጉዳትና ለማቀጨጭ ተብሎ የሚወሰድ ነው የሚያመስለው። በተለይም የተለያዩ ህብረተሰቦችን ወይም አገሮችን የማወዳደር ጥናት(Comparative Studies) ባልተለመደበት እንደኛ ባለው አገር አንድ ከዚህ ወይም ከዚያ ብሄረሰብ የወጣ ኤሊት በብሄረሰቤ ላይ ደርሷል የሚለውን ጭቆና ከጠቅላላው የህብረተሰብ ሁኔታ ጋር የማወዳደርና የማገናኘት ፍላጎትና ብቃት ስለማይኖረው በችኩል የሚወስደው ውሳኔ ወደ ማይሆን ግብግብ ውስጥ ነው የሚያስገባው።
ከዚህ ስንነሳ በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዐመታት በፖለቲካ ስም የተካሄደውን ትግል የሚባለውን ፈሊጥ ስንመለከት የተሰራው ትልቅ ስህተት የህብረተሰብአችንን ወይም የአገራችንን ዕድገት በየኤፖኩ እየነጣጠልን በመውሰድ ለአጠቃላዩ የህብረተሰብ ዕድገት ማነቆ ወይም ዕንቅፋት የሆኑ ነገሮችን በሚገባ መመርመርና ማጥናት አለመቻላችን ነው። ይህ ዐይነቱ የምርምር ጉድለት፣ ፍላጎት አለመኖርና፣ በትንሽ ዕውቀት ተደስቶና ተዝናንቶ ወደ ማይሆን ውሳኔ መድረስ የግዴታ ወደ አመጽና ቀስ በቀስም ወደ ፋሺዝም ዐይነት አመለካከት እንዲያመራ አንድን የፖለቲካ ቡድን ያስገድደዋል። ፋሺሽታዊ አመላካከትና ፋሺዝም የካፒታሊዝም ውጤት ቢሆኑም፣ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋና አዳዲስ ጥራዝ ነጠቅ ኤሊት ነን ባዮች ብቅ እንዲሉ ሁኔታውን ሲያመቻች፣ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የግዴታ ወደ አመጽና ብሎም ወደ ፋሺዝም እንዲያመራ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። ስለሆነም በአገራችን ምድር ውስጥ ካፒታሊዝም በተገለጸለት ኃይል ሳይሆን ጭንቅላቱ ባልዳበረና በተወሳሰበ መልክ ለማሰብ በማይችል የገዢ መደብ ሲገባ በአንድ በኩል ህብረተሰብአችን ለመዘበራረቅ ችሏል፤ በዚያው መጠንም አዳዲስ ጭንቅላትን የሚያድሱ አዳዲስ እሴቶች እንዳይዳብሩ ለማድረግ በቅቷል፣ በሌላ ወገን ደግም ታሪክን በተሳሳተ መልክ ለሚተረጉሙ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር ችሏል። በአብዮቱ ወቅት የተፈጸመውን ጭካኔና የርስ በስር መተራረድ ስንመለከት በጊዜው ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት ከማርክሲዝምና ከሶሻሊዝም ጋር ለማያያዝ ቢሞከርም፣ በእኔ እምነትና የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው፣ ድርጊቱ የማርክሲዝም ነጽብራቅ ሳይሆን የተኮላሸ የካፒታሊዝምና የፊዩዳሊዝም ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይልና ኢንደስርትሪየስ የሆነ ሚድል ክላስ ባላደገበት አገር ሁሉ ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ ድርጊት እንደሚከሰት ከላቲን አሜሪካ ከመሳሰሉና በሶሾሊዝም ከማይታሙ አገሮች ያየነውና ልናረጋግጥ የምንችለው ሀቅ ነው። እነ ፒኖቼትና የአርጀንቲና ጄኔራሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠር ምሁሮችና ወጣት ልጆች ላይ ጭፍጨፋ ያካሄዱት ሶሻሊስቶች ስለሆኑ ሳይሆን በተወሰነ የአሜሪካን የሚሊታሪ ሎጂክ የሰለጠኑና ኮንሰርቫቲቭ አመለካከት ስለነበራቸው ነበር። ድርጊታቸውም በሙሉ ሶሻሊዝምን ብቻ ሳይሆን የካፒታሊዝምን ዕድገት የሚቀናቀን ነበር። ስለሆነም በጊዜው በአገራችን ምድር የተከሰተውን ዘግናኝ ሁኔታ ማያያዝ የምንችለው ከሶሻሊዝም ጋር ሳይሆን ከአሜሪካን የሚሊታሪ አስለጣጠንና በጊዜው በአገራችን ምድር ከሰፈነው የሶሺዮ ኢኮኖሚ ሁኔታና ግልጽ ካልሆነና ካላደገ እንዲሁም በደንብ ካልዳበረ የመደብ ዕድገት ጋር ብቻ ነው።

በጊዜው በአገራችን ምድር የተከሰተውን አስከፊ ሁኔታ ስንመለከት፣ በአንድ በኩል አብዮቱን በሚደግፉና አዲስ ህብረተሰብ ለመመሰርት ከሚፈልገውና ከሚታገለው በሰፊው ህዝብና በነቃው ምሁራዊ ኃይል መሀከል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የአብዮቱን ውጤቶች ለመደምሰስ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በስለላ ድርጅቱ በደመገፍ በጠቅላላው በአገሪቱ ላይ የሽብር ዘመቻን ማካሄድ በጀመረው ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ዕድገት ኃይል መሀከል እንደነበር ሁኔታውን በደንብ የተከታተለ ሊያረጋግጥ ይችላል። በሌላ አነጋገር፣ የተወሰነውን የደርግ ኃይልና ከውጭ ሆኖ ወጣቶችን በማስታጠቅና በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በመመከርና በመደገፍ ሽብርና ጭፍጨፋ የሚያካሄደውን የህብረተሰብ ኃይል ስንመለከት ርዕዮተ-ዓለሙ ግልጽ ባይሆንም፣ ድርጊቱ ፋሺሽታዊ ነበር ማለት ይቻላል። የተወሰነው የህብረተሰብ ኃይልም የሶሻሊዝምን ካባ የለበሰ ቢያስመስለውና፣ ለዲሞክራሲም እታገላለሁ ቢልም ድርጊቱ በሙሉ ከሶሻሊዝምና ከዲሞክራሲ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አልነበረም። ሶሻሊዝምና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ወይም ለእነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች መታገል ግልጽነትን፣ መከራከርንና መቻቻልን እንዲያም ሲል በሃሳብ መስማማትን የሚጠይቁ በመሆናቸው ብቻ ነው። በጊዜው የነበረው ትግልም ንጹህ በንጹህ መልኩ ስልጣንን በጉልበት ለመያዝ የሚደረግ ትግል በመሆኑ ሽብርተኝነተን ያካሂዱ የነበሩ ድርጅቶች ስልጣንን ጨብጠው ምን ዐይነት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ልዩ ልዩ የአገር ግንባታ ፖሊሲዎችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ግልጽ ያደረጉት ነገር አልነበረም። ልክ ከውጭ ሆኖ  የሚጠመዝዛቸው ኃይል ያለ ይመስል ለጋርዮሽ ህብረተሰብ እታገላለሁ ያለው ኃይል በደመ-ነፍስ በመመራት አንድን ትውልድ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚያዘበራርቅና የህብረተሰቡ የማሰብና በራሱ ላይ የመተማመን ኃይል እንዲደመሰስ ማድረግ ቻለ። ይህ ሁኔታ በጠቅላላው ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቡና መዳከም እንዲፈጥር በማድረግ ህብረተሰብአዊ እሴት እንዲበጣጠስ አደረገ። አብዮቱንና ሶሻሊዝምን ይጠላ የነበረው ኃይል ይህንን የርስ በርስ መጨራረስና አገርን ማፈራረስ ከማርክሲዝም ጋር ለማያያዝ ነው የሞከረው። ነገሩን በደንብ ጠጋ ብሎ ለተከታተለና ላጠና ይህ ዐይነቱ የንዑስ ከበርቴው ድርጊት የፊዩዳሊዝምና የፔሪፈሪ ካፒታሊዝም ወይም የተዘበራረቀ ካፒታሊዝም ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ በአብዮቱ ወቅት የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት በጊዜው በአገራችን ምድር የነበረው የሶሺዮ ኢኮኖሚ ግኑኝነትና ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚገባ ያልተፍታታውና ያልዳበረው የጭንቅላት ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በዕውቀት ላይ የተደገፈ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ ጊዜው የወረቀት ትግል ሳይሆን የጠበንጃ ትግል ዘመን ነው ብሎ ወጣቱን ለማያውቀው ነገር እንዲነሳሳና የጥይት ራት እንዲሆን ማድረግ በስልጣን ጥም ከመሳከር ባሻገር አንድ ኃይል የቱን ኃይል በጥላቻ መንፈስ እንደተወጠረ ነው ሁኔታው የሚያረጋግጠው። ፋሺሺታዊ አመለካከት ያላቸውን ኃይሎች ከሌሎች ከተገለጸላቸው ኃይሎች የሚለየው መሰረታዊ ነገር በሳይንሳዊ ትንተናና በአማራጭ አስተሳሰብ እንዲሁም ክርክር ስለማያምኑ ነው። ከክርክርና ከሃሳብ መፋጨት አንድ ጥሩ ነገር ሊወጣው ይችላል ብለው ስለማያምኑ የሚያሰቅድሙት አመጽንና ግድያን ብቻ ነው። ስለሆነም የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ውስጣዊ ህግ በመጣስ ወደ አጠቅላይ ጦርነት ያመራሉ። ከመጀመሪያውኑ መቻቻል(Tolerance)፣ መደማመጥ፣ መከራከር፣ መረታትና መርታት የሚሉት ፅንሰ-ሃሳቦችን ስለማይረዳ ከነሱ የተለየ ሃሳብ ያለውን ኃይል ሁሉ እንደዋና ጠላት አድርጎ በመቁጠር ወደ ስይስተማቲክ ግድያና ቀስ በቀስም ወደ አጠቃላይ ጭፍጨፋ ያመራሉ። ሌላ አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደመሸነፍ ወይም እንደመረታት ስለሚቆጥሩ ያለው አማራጭ መንገድ ይቀናቀነኛል የሚሉትን ኃይል መግደል ወይም በመርዝ ማጥፋት ነው።

ነገሩን የበለጠ ለመረዳትና ወደ ዛሬው የወያኔ አገዛዝ ለመምጣት የወያኔ ካድሬዎች እንደሚሉት ነፃነትንና ዕድገትን በመፈለግ ወደ ጫካ የገቡ ሳይሆን በጥላቻ መንፈስ በመታወርና የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን አገነባብ ታሪክ ለመረዳት ካለማቻል በመነሳት የተደረገ በምሁር እንቅስቃሴ ያልተደገፈ የጦርነት ትግል ነው የጀመሩት። በወያኔና በሌሎች የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች ዕምነት መሰረት የአገራችንን ታሪክና የህብረተሰብ ሂደት ለስምንት መቶ ዓመታት ያህል ሊወሰን የቻለው ከአንድ ብሄረሰብ የወጣ የገዢ መደብና፣ የአንድን ብሄረሰብ ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ኃይል ነው የሚል ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የገዢ መደብ በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ የራሱን ባህል፣ ቋንቋና ልዩ ልዩ ዕምነቶች በመጫን የየራሳቸውን ባህልና ቋንቋ እንዳያዳብሩ ሊያደርጋቸው በቃ ይሉናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብቅ ባሉት የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎችና በወያኔ አገዛዝ ዕምነት መሰረት በሌሎች አገሮች የተመሰረቱት ነገስታትና በዕድገት ስም የተካሄደው ክንዋኔ በሙሉ በሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ዘንድ በስምምነት የተካሄደ ነው ይሉናል። ሌሎች አገሮች ካለምንም ውዝግብና ውጣ ውረድ ህብረተሰብን ሲመሰርቱና ዕኩልነትን ሲያሰፍኑ፣ በእኛ አገር ብቻ አንድ ብሄረሰብ የበላይነትን ለመቀዳጀት በመቻሉ የሌሎች ብሄረሰቦችን ዕድገት ሊያፍን ቻለ በማለት በዓለም አቀፍ ደረጃና፣ በተለይም ደግሞ በአውሮፓ ምድር ውስጥ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የነበሩትን ፀረ-ዲሞክራሲና ፋሺሽታዊ አገዛዞች ከቁጥር ውስጥ ባለማስገባት ወደ ተቻኮለና ፀረ-ምሁራዊ እንቅስቃሴ በማካሄድ አነሰም በዛም ለፋሺዝም የሚያመች ሁኔታ ለመፍጠር ችለዋል ማለት ይቻላል። በሌላ ወገን ግን ይህንን አስተያየታቸውን ሲሰነዝሩና የጥላቻ መንፍስን ሲያስፋፉ የየብሄረሰቦቻቸውን የማቴሪያል ዕድገትና የባህል ደረጃ ሊያብራሩልን በፍጹም አልቻሉም። በየብሄረሰቦቻችው ውስጥ የነበሩት አገዛዞች ምን ይመስሉ እንደነበሩ፣ በስራ-ክፍፍል ላይ የዳበረ የገበያ ኢኮኖሚ ይኑር አይኑር፣ በግለሰብ ላይ የተመሰረተ የነፃ ገበያ ክንዋኔ ይኑር አይኑር፣ በየክልላቸው ውስጥ ይህንን የገበያን ኢኮኖሚ የሚያሰተሳሰር አንድ ዐይነት ገንዘብ ይኑራቸው አይኑራቸው፣ የተፈጥሮ ሀብትንና የሰውን ጉልበት ለማንቀሳቀስ የሚችሉ ኢንስቲቱሽኖች ይኑራቸው አይኑራቸው፣ የሚግባቡበት በጽሁፍና በቃላት የሚገለጽ የዳበረ ቋንቋ ይኑራቸው አይኑሯቸው… ወዘተ. ወዘተ፣ እነዚህን ሁሉ እያብራሩ ሊያስረዱን በፍጹም አልቻሉም። ዝም ብለው ብቻ በጥላቻና በዝቅተኛ ስሜት በመነሳት፣ በተለይም ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ የሃያኛው ክፍለ-ዘመን ኤሊቶች አጠቃላይ ጦርነት አወጁ። በተለይም በአንድ ብሄረሰብ ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ ማካሄድ ጀመሩ።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔ አገዛዝ በአንድ በኩል የታሪክን ውጣ ውረድነት ያለገናዘበ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እጅግ በዝቅተኛ ስሜት በመወጠሩ የተነሳ ሳይወድ በግድ ወደ እንደዚህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ትርምስ ውስጥ ሊከተን ችሏል። ይሁንና ግን ይህንን ዐይነቱን ፋሺሽታዊ ድርጊት ለመፈጸም የግዴታ የአገራችን ነባራዊና የስነ-ልቦና ሁኔታ በራሳቸው በቂ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም። እንደሌሎች በ1970ዎቹ ዓመታት ብቅ እንዳሉ ፋሺሽታዊ አገዛዞች በተስፋፋባቸው እንደላቲን አሜሪካ በመሳሰሉት አገሮች የወያኔ አገዛዝም ሌጂቲሜሲ ለማግኘትና ፈሺሽታዊ አገዛዙን ለማስፈንና የአገራችንን ዕድገት ለመጎተት ሲል የግዴታ የውጭ ድጋፍ አስፈልጎታል። የአገርን ዕድገትና የህዝባችንን መተሳሰር  ከሚጠሉ የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችና የስለላ ድርጅቶች የገንዘብና የሞራል ድጋፍ በማግኘት ነው ወደ ፋሺዝምነት ሊያመራ የቻለው። በሌላ አነጋገር፣ የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ስልጣንን መቆናጠጥ ካለ አሜሪካንና ካለ እንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ውጭ በፍጹም ሊታሰብ የሚችል አይደለም። ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ተግባራዊ ያደረገውን የኒዎ-ሊበራል ወይም የተቅዋም መስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ (Structural Adjustment Program) በምንመለከትበትና በምንመረምርበት ጊዜ እነ ፕሬዜዴንት አሌንዴ በ1973 በእነ ጄነራል ፒኖቼት ከተገደሉ በኋላ ተግባራዊ ካደረጉት የኒዎ-ሊበራል ወይም የማርኬት ራዲካሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ናኦሚ ክላይን ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የ ሾክ ዶክትሪን እያለች የምትጠራው ሲሆን፣ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ለማደለብ የቻለና ፈሺሽታዊ አገዛዝን እንዲጠናከር ያደረገ ነው። ይህም ማለት ምን ማለት ነው ? በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮች ዕምነት መሰረት ወያኔ ስልጣን ለመያዝ እስከበቃ ድረስ በአገራችን ምድር ይካሄድ የነበረው የሶሻሊስት ዕዝ ኢኮኖሚ በመሆኑና፣ ይህም ፖሊሲ ተፈጥሮአዊ የሆነውን የገበያ ኢኮኖሚና የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ጥቅም የሚፃረር በመሆኑ ተወግዶ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መተካት አለበት። በዚህም መሰረት ናኦሚ ክላይን እንዳለቸው የህብረተሰቡ ጭንቅላት እንዳለ በመበወዝና በመታጠበ ከሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በመላቀቅ በገበያና በሸቀጣ ሸቀጥ የኢኮኖሚ መተካት አለበት፤ ዕምነቱም ይህ መሆን አለበት የሚል ነው። ስለሆነም ወያኔ ስልጣን ሲይዝ ይህንን ዐይነቱን ጠቅላላውን ህብረተሰብ ጭንቅላቱን የሚበውዝና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የሚያደልብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ተግባራዊ እንዲያደርግ ምርጫ የቀረበለት። ስልጣንም ላይ ሊወጣ ይችል የነበረው ይህንን ዐይነቱን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ብቻ ነበር። ስለሆነም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና የወያኔ ፋሺዝም የሚደጋገፉና አንድ ላይ ተያይዘው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው። አንደኛውን ከሌላው መነጠል በፍጹም አይቻልም። የአገራችንንም ተጨባጭ ሁኔታና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የስነ-ልቦና ወይም የህሊና አውቃቀር ሁኔታ ስንመለከት በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ህብረተሰብአችን የቱን ያህል እንደተዘበራረቀና ገንዘብ ዋናው መለክያ በመሆን የሰው በሰው ግኑኝነትና ፍቅር በገንዘብ የሚተመኑ ሊሆኑ የበቁበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ሰርቶና ፈጥሮ ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ማጭበርበርና መካካድ ዋናዎች የህብረተሰብ ኖርሞች በመሆን በህዝብ ዘንድ መቃቃርን እንዳስከተሉ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ያረጋግጣል። ከዚህም በላይ አዳዲስ የአኗኗር ስልቶችና ሲሌብሪቲ የሚባለው የመተያያና የማሸብረቂያ ሁኔታ ከአሜሪካን እንዳለ በመቀዳቱ የተነሳና በመስፋፋቱ የህብረተሰብአችንን እሴት በከፍተኛ ደረጃ እንዳናጋውና ሰፊው ህዝብ ዕውነተኛውን የኑሮ ትርጉም እንዳይረዳ እንዳደረገው ማረጋገጥ ይቻላል። ናኦሚ ክላይን እንዳለቸው በዚህ መልክ የህዝባችን ጭንቅላት፣ በተለይም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ጭንቅላት በገንዘብ ናላው እንዲዞር ሲደረግ፣ ማንነቱን በመሳት ሰውን መናቅና አገርን ማፈራረስ ችሏል።

በመሆኑም በአንድ በኩል መንግስታዊ መዋቅሮችን ለራስ በሚመች መንገድ ማዋቀርና ወደ ጨቋኝ መሳሪያነት መለወጥ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን የጭቆና መሳሪያና አገዛዝ የሚያጠናክር የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ አንድ ላይ የሚሄዱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በተደረገባቸው አገሮች በሙሉ አነሰም በዛም፣ በተለያየ ጥንካሬ መንግስታት በሙሉ ወደ ዲሞክራሲና ግለሰብአዊ ነፃነት፣ እንዲሁም ወደ ተስተካከለ ዕድገት ያመሩ ሳይሆን፣ ወደ ዘራፊነት(Predatory States)፣ ወደ ተመሰቃቀለ ህብረተሰብና በከፍተኛ የአካባቢ ቀውስ በሚገለጽ ማህበረሰብ ነው ማምራት የቻሉት።  ወያኔን ስልጣኑን ለማጠናከር የቻለበት ሌላው ምክንያት ደግሞ በብሄረሰብ ስም አሳቦ የሚያካሄደው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲና በየቦታው ዋር ሎርዶች(War Lords) እንዲፈጠሩ በማድረጉ ነው። እነዚህን በጥቅም በመግዛትና በአንድ ብሄረሰብ ላይ እንዲነሱ በማድረግ የራሱን ኃይል ለማጠንከርና ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ለማከማቸትና የተወሰነውን ደግሞ ወደ ውጭ ለማሽሽ ዕድል ለማግኘት ችሏል። በዚህ መሰረት በየቦታው ያስቀመጣቸው ታዛዦች እናስተዳድራለን በሚሉት ክልል ውስጥ እነሱ የተደላደለ ኑሮ ሲኖሩና እንደ ንጉስ ሲታዩ፣ ምስኪኑ ህዝብ ደግሞ ወደ ጨአትና አበባ ተካይነት በመዳረግ የዚህ ዐይነቱ ያልተሰተካከለ ዕድገት ሰለባ በመሆን ተፈጥሮአዊ መብቱን እንዲገፈፍ ተደርጓል።
ያም ሆነ ይህ ዛሬ በአገራችን ምድር ፋሺዝም ወይም ደግሞ አንዳንዶቹ እንደሚሉት የኤትኒክ ፋሺዝም ሰፍኗል ማለት ይቻላል። በተለይም ይህንን አስተሳሰብ የሚያጠናክረው ሌላው ዋና ምክንያት እንደሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች የትግሬ ብሄረሰብ ያልተሰበጣጠረና(Undifferntiated) እንዲሁም በልዩ ልዩ የስራ-ክፍፍል የሚገለጽ ማህበረሰብ ባለመሆኑና፣ ፓትሪያሪካልም ስለሆነ ይህ ሁኔታ ወደ አምባገነንነትና ብሎም ወደ ፋሺዝም እንዲያመራ አስገድዶታል። በተለይም በወንዶችና በሴቶች መሀከል ያለውን ግኑኝነት ስንመለከት ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጋር ሲወዳደር ጭቆና የበዛበትና ሴቶችን በንቀት የሚታዩበት ክልል ነው ማለት ይቻላል። አንዳንዶች ምናልባት በዚህ ዐይነቱ አባባል ላይስማሙ ይችሉ ይሆናል። ችግሩ ግን የአገራችንን ሁኔታ ከሂትለሩ የናዚ አገዛዝ ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ ሊጣጣሙ  የማይችሉ መስሎ ይታየናል። አውሮፓ ውስጥ የተካሄዱት ከዘር ማጥፋት ጋር የተያያዙ ፖለቲካዎች በሙሉ በቲዎሪና „ በሳይንስ “ የተደገፉ በመሆናቸው ግራ ሊያጋቡን ይችላሉ። የአርያን ዘር የተመረጠ፣ ያልተቀላቀለና መሳሪያዎችንም ለመፍጠርና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ተስጥዖ አለው ተብሎ ይሰበክ ስለነበር፣ ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ ቅስቀሳ በአገራችን ምድር የተለመደ ባለመሆኑ የወያኔን አገዛዝ እንደ ፋሺዝም መቁጠር አይቻልም የሚሉ ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። ፋሺዝም በመሰረቱ በተቀነባበረና በመንግስት የሚደገፍ የጭፍጨፋ ተግባር ስለሆነ በአገራችንና በጀርመኑ ፋሺዝም መሀከል ያለው ልዩነት የዐይነት ወይም የይዘት ሳይሆን የዕድገት ደረጃ ብቻ ነው። ነገሩን በዚህ መልክ ብቻ ነው መረዳት ያለብን።

ይህ ዐይነቱ አተናተን ወይም አቀራረብ በተለይም ስልጣንን ለመካፈል የሚፈልጉ ወይም የሚታገሉ ኃይሎችን ወይም ደግሞ ክሪቲካል ቲዎሪ ምን እንደሆነ የማያውቁትን ሊያሳምን አይችልም። በተለይም እንደ አገራችን ባለው ህብረተሰብ ውስጥና ክሪቲካል ቲዎሪና አመለካከት ባልዳበረበት አገር በየጊዜው የሚከሰቱትን የፖለቲካ አሰላለፎች(Political Power Relationship)፣ የህብረተሰብ ግኑኝነትና(Social Relationship) የምርት ግኑኝነት ጠጋ ብሎ በመመርመር ዕድገትን በሚፈልጉና ዕድገትን በሚቀናቀኑ ኃይሎች መሀከል ያለውን ግብግብና የሃሳብ ልዩነት ለማይረዱ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ግብግቡን እንደተራ የፖለቲካ ሽኩቻ አድርገው ነው የሚመለከቱት። ክሪቲካል ቲዎሪ ሲባልም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለውን በስልጣን አካባቢ የሚደረገውን ሽኩቻ ከመመርመር ባሻገር፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በየጊዜው የሚወሰዱ የፓለቲካ ዕርምጃዎችን፣ የሀብት ጥያቄና-በተለይም መሬትን መቆጣጠርና ቀስ በቀስም ህጋዊ በማድረግ አብዛኛውን ህዝብ ከመሬት እንዲገፋ ወይም ጭሰኛ ማድረግ- ይህ በራሱ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ የፀረ-ዕድገትና የዕድገት ሁኔታዎች የመመርመሪያ ዘዴ ነው። ክሪቲካል ቲዎሪ ከሁለት ሺህ ዐመት በፊት የዳበረና የተስፋፋ ቢሆንም፣ – ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ፍልስፈና በመጠየቅና መልስ ለመፈለግ በመጣር ነው
ሊዳብሩ የቻሉት አብዛኛውን ጊዜ ከማርክሲዝም ጋር የተያያዘ የህብረተሰብ መመርመሪያ፣ በተለይም በካፒታሊዝም ውስጥ የተደረገውን የኃይል አሰላለፍ፣ የፍጆታ አጠቃቀምና ጠቅላላውን ህብረተሰብ በሽቀጣ ሸቀጥ የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ ለማጠቃለልና የየግለሰቦች አስተሳሰብም በአንድ የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ እንዲሽክረከር ለማድረግ የታቸለውን አጠቃላዩን የካፒታሊዝምን ስልተ-ምርት ክንዋኔ መመርመሪያ ዘዴ ነው። በተለይም ዘመናዊነት ያመጣውን ከቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር የተፈጠረውን አስተሳሰብ፣ እነ ማርኩዜ እንደሚሉት በፍጆታ አጠቃቀምና በገንዘብ ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት በተለይም ሰፊውን ወዝ-አደር ትችታዊ በሆነ መልክ እንዳያስብ ሊያድረገው በቅቷል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ልቅ የሆነ የፍጆታ አጠቃቀምና በራስ ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮረ ግለሰብአዊነት መስፋፋት ለቶታሪያሊንዝም ወይም ለፋሺሽታዊ አገዛዝ መነሾ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህ ቲዎሪ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የፍራንክፈርት ትምህርት በሚባሉት በአዶርኖ፣ ሆርክሃይም፣ ማርኩዜ፣ ወደ ፈረንሳይ ስንሄድ ደግሞ የስትራክቸራል አስተሳሰብ አፍላቂዎች(Structural school of Thought) በሚባሉት በአልቱዜር፣ በባሊባርና በፎኮልት የዳበረ የአንድን ህበረተሰብ አጠቃላዩን ዕድገትና ክንዋኔ መመርመሪያ ዘዴ ነው። ይህ ዐይነቱ ሰፋ ያለና የዳበረ የህብረተሰብ ክንዋኔና ዕድገት መመርመሪያ ዘዴ በእኛ አገር ባለመስፋፋቱና የተለመደ ባለመሆኑ በአገራችን ምድር በየጊዜው የሚከሰቱ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፎችን ሁኔታና የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጦች የሚያደርስቱን አሉታዊ ውጤቶች ስነስርዓት ባለው መልክና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ለመመርመር የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በመሆኑም ለፖለቲካ ስልጣን ወይም ለነፃነት እታገላለህ የሚል ድርጅት ወይም ግለሰብ በሙሉ ካለምንም መመሪያ ወይም ቲዎሪ እዚህና እዚያ ስለሚራወጥ ራሱ ተደናብሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የዋህ ሰዎችንና ታዳጊ የህበረተሰብ ክፍልን ግራ ያጋባል። ትግሉም ምሁራዊና ዕውነተኛ ነፃነትን አምጭ መሆኑ ቀርቶ በጭፍን የሚካሄድ በመሆኑ ልንወጣው የማንችለው ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ ሊያደርገን በቅቷል። የወያኔም የስልጣን አያያዝና ስልጣንም ከያዘ በኋላ የሚወስዳቸው የተደናበሩ ፖሊሲዎችን መዋጋት ያልተቻለው ግልጽ የሆነ የምንመራበት ፍልስፍናና ቲዎሪ ባለመኖሩ ብቻ ነው።
ያም ሆነ ይህ የወያኔ አገዛዝ የመንግስቱን መኪና፣ ማለትም ሚሊታሪውን፣ ፀጥታውን፣ ፓሊሱንና የሲቪል ቢሮክራሲውን በመቆጣጠር የሚገለጽ ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር ከትግሬ ብሄረሰብ የተመለመሉና ጠበንጃ የታጠቁ አፋኝ ኃይሎች በየቦታው በመሰማራት የአገዛዙን የበላይነት ያረጋግጣሉ። በዚህም መሰረት የወያኔ አገዛዝ ቀደም ብሎ በገበያ የኢኮኖሚ ስም ወደ ግል-ሀብትነት የተዘዋወሩ የኢኮኖሚ አውታሮችን በመቆጣጠርና፣ ታታሪ ኃይሎችን በማግለልና ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር በመተሳሰር የተወሳሰበ የአገዛዝና የብዝበዛ መዋቃር ዘርግቷል ማለት ይቻላል።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ባላፉት 27 ዓመታት በመደብ ላይ ሳይሆን በጎሳ ላይ የተመሰረተ የጭቆናና የብዝበዛ ስርዓት ሰፍኗል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ከትግሬ ብሄረሰብ ከተውጣጣ ኃይል ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ወደድንም ጠላንም በተለያዩ መልኮች የሚገለጽ፣ ግን ደግሞ ምሁራዊነትና ሳይንሳዊነት የጎደለው የትግሬን የበላይነት ማስፈን ነው። በሌላ  አነጋገር፣ አገዛዙ ጠባብ አስተሳሰብ ስላለውና በዝቅተኛ ስሜት የሚመራ በመሆኑ እንደ ከበርቴው የካፒታሊስት መደብ ጠቅላላውን ህብረተሰብ ሊይዝበትና ሊገዛበት የሚችልበት መሳሪያ የለውም። በሌላ ወገን ግን ይህንን አስመልክቶ ሰሞኑን የህወሓት የበላይነት እንጂ የትግሬ የበላይነት የለም እየተባለ በአንዳንዶች የነሱ አፈ-ቀላጤዎችና ሌሎች አድር- ባዮች ወይም ደላሎች ሲስተጋባ ይሰማል። ይህንን ዐይነቱን አስተሳሰብ የቀን ተቀን አፈናና ጭቆና፣ እንዲሁም ግድያ ለሚፈጸምበት ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ማስረዳትም፣ ማሳመንም በፍጹም አይቻልም። ስለሆነም ሰፊው ህዝብ አገዛዙና እዚህና እዚያ ተሰግስገው የአፈና ስራ የሚያካሂዱትንና፣ ካለምንም ልፋት ወይም ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘረፋ ሀብታም የሆኑ ትግሬዎችን ሁኔታና፣ ግልምጫቸውንና መዘባነናቸውን ከጠቅላላው ትግሬ ብሄረሰብ ጋር ነው የሚያይዘው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በታሪካችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተና መረን የለቀቀ በመሆኑ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁኔታውን ከወያኔ ጋር ሳይሆን ከትግሬ የበላይነት ጋር ማያያዝ መቻሉ የሚያስገርም ሊሆን አይችልም። በተለይም በትላልቅ ሆቴል ቤቶች በመግባትና በአንድ ምሽት ውስጥ እስከ አስር ሺህና ሃያ ሺህ ብር ድረስ ለብሉ ሌብል ውስኪና ለልዩ ዐይነት ኮኛክ ማፍሰስ፣ ከህዝቡ ተነጥሎ በአንድ አካባቢ በመኖር በዚያ አካባቢ ያለውን ህዝብ መጋፋትና ማስፈራራት፣ ወደድንም ጠላንም እነዚህ ሁሉ በትግሬ የበላይነት ከዕውቀትና ከማሰብ ጉድለት የተነሳ የሚገለጹ ድርጊቶች ናቸው። ስልሆነም በዚህ ላይ የሚደረገው የማያስፈልግ ክርክር ሁኔታዎችን በግልጽ እንዳናይ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ግልጽ የሆነ ዕውነተኛ የመንፈስ ነፃነትን የሚያመጣ ፖለቲካዊና ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳናካሂድ ያግደናል። ይህንን ዐይነቱን መረን የለቀቀ ሁኔታ የትግሬ ምሁራን ማረም መቻል ነበረባቸው። እንደምከታተለው ከሆነ በስልጣን አካባቢ በሌሉት ምሁራንና በየቢሮው ውስጥ በተሰገሰጉት አመለካከት መሰረት የአገዛዙን ድርጊት ትክክል ነው ብለው የሚቀበሉ ናቸው። ዘመኑ የትግሬ የበላይነት የሰፈነበት ስለሆነ በዚህ ዐይነቱ የጭቆናና የግድያ ድርጊት ካልገፋንበት የበላይነታችንን በፍጹም ማረጋጥ አንችልም የሚል በሁሉም ዘንድ ውስጣዊ ስምምነት(Tacit Areement) አለ ። እንደዚህ ስል ግን ህዝቡ በትግሬ ብሄረሰብ ላይ እንዳለ ይነሳበት ማለቴ አይደለም። ይህንን ሁኔታ ሊያርምና ህዝቡን ሊያስተምር የሚችለው የተገለጸለት የትግሬ ምሁርና የነቃው ክፍልና ራሱን ከልዩ ልዩ ምስቅልቅል ሁነታዎች ያፀዳው የትግሬ ምሁር ብቻ ነው። በተቻለ መጠን በጥሩ ቋንቋ ህዝቡን ማስተማርና አገዛዙን ከህዝባቸው በመነጠል ተከባብሮ ለሚኖርና ዲሞክራሲያዊ ለሚሆን ህብረተሰብ መታገል ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታው መሆኑን መረዳት አለበት። ማንኛውም ነገር ጊዚያዊ እንደመሆኑ መጠን የወያኔ የበላይነት በቀላሉ ሊፈረካከስ ወይም ሊደመሰስ የሚችል በመሆኑ ቸል ሳይሉ ያልተቆጠበ ትግል በማድረግ ታሪካዊና ህብረተሰብአዊ ግዴታቸውን መወጣት መቻል አለባቸው።

ነገሩን መቋጠሪያ ለማስያዝ፣ አገራችንን ነፃ ለማውጣት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት አድርጎ በብዙ ነገሮች የሚገለጽ ህብረተሰብ ለመገንባት የምንፈልግ ከሆነ በውስጥ ባለው አገዛዝና በውጭው ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል መሀከል ያለውን መተሳሰርና የእከክልኝ ልከክልህ መተጋገዝ ፖለቲካ መረዳት አለብን። የውጭውን ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይልና ለአገዛዙ የሚሰጠውን ድጋፍ ከፖለቲካ ስሌታችን አውጥተን በወያኔ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ፖለቲካ የምናካሂድ ከሆነ ወደድንም ጠላንም እኛም በሌላ መልክ ለሚገለጽ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ወይም አምባገነናዊ አገዛዝ ነው የምንታገለው ማለት ነው። ስለሆነም የግዴታ በውጭውና በወያኔ መሀከል ያለውን በጥቅም መላላስና ፀረ-ዕድገትና ፀረ-ዲሞክራሲ ፖለቲካ መረዳቱ የጊዜው አንገብጋቢ መሰረተ-ሃሳብ ነው እላለሁ። ከዚህም በሻገር በአገራችን ምድርና በአካባቢው የሚካሄደው ጦርነት በራሱ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረ-አበሮቹ የተቀነባበረ ፀረ-ዕድገት፣ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ ድርጊት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ባለፈው ጽሁፌ፣ „ ጦርነቱ
የአፍሪካውያን  አይደለም የአሜሪካንና የአውሮ ፓ ውያን ጦርነት  ነው “ በሚለው ውስጥ ለማሳየት እንደሞከርኩት አገራችንም እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች በጦርነት መተረማመስ አለባት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለዕድገት የሚደረገው ትግል ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ደብዛው የሚጠፋው። ይህ የአሜሪካንና የግብረአበሮቹ ዕምነት ነው። ስለሆነም በሌላ አፍሪካ ምድር ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ለኛ የሚያስቡበት አንዳችም ምክንያት የለም። ይህንን ጒዳይ መረዳቱ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ስለሆነም በአታላይ ኃይሎች መታለል የለብንም፤ የነገሩን ውስብስብነት በመረዳት በግልጽ መነጋገርና ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ስልጣኔ ኃይሎችን መጋፈጥና በሳይንሱ ማጋለጥ የጌዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ከወያኔ ጋር አብሮ በመስራት ወይም የአገዛዙ አንድ አካል በመሆን መስረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ወይ ?

ይህንን አመለካከት የሚያስተጋቡ፣ ወይም „ አገዛዙ የችግሩ ዋና ምክንያት ራሱ ስለሆነ እራሱም የመፍትሄው አንድ አካል መሆን አለበት “ ብለው የትልቅ ወይም የጨዋ ሰው አስተያየታቸውን የሚሰነዝሩ ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን ገለጻ ስስማ፣ እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል በአገራችን ምድር በህዝባችን ላይ ለ27 ዓመታት የደረሰውን ጭፍጨፋ፣ መሰደድና  መጎሳቆል በደንብ ጠጋ ብለው የመረመሩ አይደሉም፤ በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ዐይነቱ አባባላቸው ስለህብረተሰብና ስለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ነው የሚያረጋግጠው። በተለይም በአገዛዙ አማካይነት በሃይማኖት ስም ተሳቦ ግጭት ተካሄደ፣ ስንትስ ህዝብ አለቀ ፟? በአገዛዙ ፖሊስስ አማካይነት ስንትስ ህዝብ ከቤቱ እየተፈናቀለ ለጅብ እንዲዳረግ ተደረገ? ስንትስ ህዝብ ዘመናዊ እርሻን ለማስፋፋት ሲባል ከመሬቱ በመፈናቀል ወደ ጎረቤት አገሮች ወይም ወደ ከተማዎች እንዲሰደድ ተደረገ ብለው? ጠይቀው ያውቃሉ ወይ። በመሰረቱ እንደዚህ አልኩ ለማለት ካልተባለ በሰተቀር ይህ ዐይነቱ አባባል ምንም ዐይነት ሎጂክ የለውም። በሳይንስም ሆነ በቲዎሪ የሚደገፍ አይደለም።

አንደኛ፣ አገዛዙ ተግባራዊ ያደረጋቸው የክልል ፖሊሲዎች የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ዋናው አካል ናቸው። በአገዛዙም ዕምነት አንድ ማህበረሰብ ርስ በርሱ ሲጠራጠርና መተማምን ሳይኖር፣ እንዲያም ሲል ወደ ርስ በርስ ጦርነት ሲያመራ ብቻ ነው ስልጣን ላይ ለብዙ ዘመናት እቆያለሁ ብሎ የሚያምነው። ይህንን ዐይነቱን አንድን ህብረተሰብ በቋንቋ በመከፋፈል የአገራችንን ዕድገት ወደኋላ እንዲሄድ ያደረገው ከዚህ ስሌት በመነሳት እንጂ የየብሄረሰቦችን ዕድገት በመፈለጉና ኑሮአቸው እንዲሻሻሉ በመሻቱ አይደለም። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲና ለአንዳድን ብሄረሰቦች ደግሞ ፊደል እየቀረጹ በህዝቡ ዘንድ መግባባት እንዳይኖር ማድረግ እንግሊዞች የፈጠሩት ተንኮል ነው። አንድ ህዝብ ሊግባባበት የሚችል ቋንቋ ከሌለው ሃሳብ ለሃሳብ ሊለዋወጥና እንደ ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሆን በአንድ ላይ በመንቀሳቀስ ለዕድገት መነሳሳት አይችልም። ይህንን ዐይነቱን የኢምፔሪያሊስቶች ተንኮል ነው ወያኔ በተግባር የመነዘረውና በብሄረሰቦች መሀክል መግባባት እንዳይፈጠር ያደረገው። ስለሆነም ይህንን ዐይነት ተንኮል ሆን ብሎ የፈጠረ ኃይል የችግሩ መፍትሄ ሊሆን በፍጹም አይችልም።

በሁለተኛ ደረጃ፣ በዚህ አማካይነት በየቦታው ዋር ሎርዶችን ስልጣን ስጥቶና እንዲደላደሉ አድርጎ ህብረተሰቡ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ግንባታና ኢንስቲቱሽኖችን በመመስረት ያለውን ሀብት እንዳያንቀሳቅስ ማድረግ የፀረ-ዕድገት አንደኛው ስትራቴጂ ነው። በመሆኑም በኒዎ-ሊበራሊዝም ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ የዚህ አገርን የማድቀቅ ከፍተኛው የፖሊሲው አካል ነው። አንድ ህብረተሰብ ሁለ-ገብ የሆነ ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳያደርግ ከታገደ ወደ ማህበረሰብና ወደ ተጠናከረ ህብረተሰብ ሊያመራ አይችልም። ባጭሩ የወያኔ አገዛዝና ደጋፊዎቹ የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ይህንን ዐይነቱን የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚጻረር ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲን ነው ተግባራዊ በማድረግ ህዝባችንን የባሰውኑ ወደ ድህነትና ወደ ረሃብ የገፈተሩት። ከዚህ ስንነሳ በምን ተዓምር ነው አገዛዙ የችግሩ አንድ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው? ይህንን ሎጂክ ከአገዛዙ ጋር መስራት አለብን የምትሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች አስረዱን።

ከዚህ ስንነሳ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ህዝብና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በወያኔና በግብረአበሮች መሀከል ህብረተሰብንና ጠንካራ ኢኮኖሚን ገንብቶ የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር የሰማይና የምድርን ያህል ልዩነት ነው ያለው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘው የተከበረችና የተረጋጋች አገርን መገንባት ነው። ህዝባችን የሚመኘው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ርስ በርሱ የተሳሰረ ኢኮኖሚ መገንባትን ነው። በዚህ አማካይነት ብቻም ለተከታታዩ ትውልድ ታሪክ ያለው አገር ማስተላለፍ ይቻላል ብሎ ነው የሚያምነው። ይህንን የተቀደሰ የህዝባችንን አመለካከትና ምኞት ወያኔና የሚደግፉት እምፔሪያሊስት ኃይሎች አጥብቀው ይቃወማሉ። የነሱ ምኞት የተሽመደመደች አገርና፣ ደሃንና ለማኝ ህዝብን ነው ማየት የሚፈልጉት። በመሆንም እኛና የኢትዮጵያ ህዝብ ከነዚህ ክቡር ኢትዮጵያውያን የሚሰነዘረውን አንድን አገር ለዝንተዓለም በድህነት የሚያስቀረውን አብሮ የመግዛት ምኞትና አገዛዙን መለማመጥ ሃሳብ በፍጹም አንቀበለውም። ሁኔታውም በመቻቻልና በእርቅ(National Reconciliation) የሚፈታ አይደለም። አገዛዙ በሀብትና በሚሊታሪ ኃይል የፈረጠመ ስለሆነ ራሱ የፈጠረውን ችግር በኃይል ብቻ ነው እፈታለሁ ብሎ የሚያምነው። በአገዛዙ ጭንቅላት ውስጥ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች፣ መከራከርና ማሳመን፣ እንዲሁም በተወሰነ የሃሳብ ክልል አብሮ በመስራት ችግርን እፈታለሁ ብሎ የሚያምን አይደለም። የሚያምነው በማሸነፍና በመሽነፍ ብቻ ነው። ስለሆነም በጠብንጃ ኃይል ተጋፈጡኝ የሚል አምርሮ የተነሳ ኃይል ነው። መንፈሳዊ ኃይሉ በዘረፈው ሀብትና በተንደላቀቀ ኑሮ ተሟጦ ያለቀ በመሆኑ የፖለቲካ ትርጉምን የሚረዳ ኃይል አይደለም። ፖለቲካ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብም ጭንቅላቱ ውስጥ ያለ አይደለም። ፖለቲካን የሚረዳው የተንኮል መሳሪያና አንድን ህዝብ ማስፈራሪያና መበወዣ አድርጎ እንጂ ጥበባዊና አንድን ህብረተሰብ በስነ-ሰርዓት ማስተዳደሪያ መሳሪያና የታሪክ መስሪያ አድርጎ አይደለም የሚረዳው። ይህንን የአገዛዙን ባህርይ እንዴት መረዳት ያስቸግራል ? ከዚህ ስንነሳ ጉዳዩ የመቻቻልና ያለመቻቻል ሳይሆን ሁለንታዊ ዕድገትን፣ ዲሞክራሲንና ሰላምን በሚጠላው በወያኔና በግብረአበሮቹ መሀክልና፣ በሌላ ወገን ደግሞ ስላምን፣ ዕድገትንና ዲሞክራሲን በሚመኘውና ዕውን ለማድረግ በሚፈልገው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ መሀከል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያምነው በአገራችን ምድር ሰላምና ብልጽግና ሊሰፍኑ የሚችሉት ከዚህ አገዛዝ በኋላና ባሻገር ብቻ ነው ብሎ ነው። በመሆኑም በሌላ መልክ በኢምፔሪያሊስቶች ተጠንስሶና ተዘጋጅቶ የነሱን ጥቅም የሚያስጠብቀውን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውንም ኃይልም በፍጹም አይቀበልም።

ስለሆነም ትግላችን ይህንን አገዛዝ በመለማመጥ፣ ወይም በኢምፔሪያሊስቶች ጓዳ ውስጥ ገባና ወጣ በማለት ሳይሆን ዕውነተኛ ነፃነት የሚገኘው በማያቋርጥ ጭንቅላትን በሚያፀዳ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ወደ ተግባር በሚለወጥ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። ትግሉም ሁለ-ገብ የሆነና ጠቅላላውን ህዝብ የሚመለከት መሆን አለበት። በብሄረሰብ ስምና ነፃነት የሚካሄድ ትግል መሆን የለበትም። ግለሰብአዊ ነፃነትንና ድርጊትን ተግባራዊ እንዲሆን የሚያደርግና ለብሄራዊ ሀብት ዕድገት የሚያመች ሁኔታ ሲፈጠር ጠቅላላው ህዝብ ተጠቃሚ መሆን ይችላል። አንድ አገር ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ስትችል ብቻ ነው አንድ ህዝብ ነፃነቱን መቀዳጀት የሚችለው። በተቃራኒው ግን በብሄረሰብ ላይ የሚደረግ ትግል ሳይንስንና ቴክኖሎጂን እንዲሁም ሁለ-ገብ የሆነን የኢኮኖሚ ዕድገትን ስለሚቀናቀን በየክልሉ ውስጥ ያለ ብሄረሰብ አበባና ጨአት እንዲሁም ቡና ከማምረት ውጭ ሊያስብ አይችልም። ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ደግሞ ዕውነተኛ የስራ-ክፍፍልን የሚፃረር ነው። የህዝቡን የመፍጠር ኃይል የሚያፍን ነው። አዳዲስ መሳሪያዎችን በመፍጠርና በመስራት ወደ ከፍተኛ ህብረተሰብ እንዳይጓዝ ወይም እንዳያድግ የሚያግደው ነው። ስለሆነም ትግላችን ከዚህ አገዛዝ ባሻገር መሆን አለበት እንጂ ከሱ ጋር አብሮ በመስራት አይደለም የተወሳሰበው የአገራችን ችግር የሚፈታው። መልካም ግንዛቤ !

 fekadubekele@gmx.de