[gtranslate]

ፖለቲካ በፍልስፍና መነፅር ሲመረመር !

                                                        ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

                                                      ሚያዚያ   09 2019

መግቢያ

አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን  በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ከብራዚል ጀምሮ እስከ አርጀንቲናና ሜክሲኮ እንዲሁም በጠቅላላው ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ቀውስ ይታያል። እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ መጥቆ በሚገኘውና በካፒታሊስታዊ የስልተ-ምርት ክንውን  በሚደነገገው አሜሪካና እንዲሁም አውሮፓ ምድር ውስጥ እንደየሁኔታው ከፍተኛ የፓለቲካ አለመረጋጋት ይታያል። በተለይም የስድሳና የሰባ ዐመታት የፓርቲ አወቃቀርና የፖለቲካ ልምድ ባላቸው እንደጣሊያንና ፈረንሳይ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የክርስቲያን፣ የኮሙኒስትና የሶሻሊስት ፓርቲዎች በመፈረካከስ የፖለቲካ መድረኩ በአዳዲስ ርዕያቸውና ቅርጻቸው በደንብ በማይታወቁ የግለሰቦች ስብስብ ተተክቷል።  ይህም የሚያሳየው ወደፊት በብዙ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትርምስ እንደሚከሰትና፣ በየአገሮችም ውስጥ ሆነ በየአካባቢያቸው አለመረጋጋት እንደሚፈጠር ነው።

የኮሙኒስቱ ብሎክ ከፈራረሰና በዓለም አቀፍ ደረጃም የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ መርሆች በአሸናፊነት ወጡ ከተባለ 29 ዐመት ሊሆነው ነው። እ.አ እስከ 1989 ዓ.ም በሁለት ኃያላን መንግስታት የተከፋፈለው ዓለም በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካና የማህበራዊ ሁኔታ አለመረጋጋትን እንዳስከተለ ሲወራና እኛም አምነን እንደተቀበልነው የማይካድ ሀቅ ነው። ስለሆነም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የኮሙኒስቱ ብሎክ ከፈራረሰና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካፒታሊዝምና የሊበራል ዲሞክራሲ ከታወጁ ወዲህ የዓለም ህዝብ ወደ ሰላምና ወደ ብልጽግና ያመራሉ ተብሎ የታመነበትና ተቀባይነትም እንዳገኘ የማይታበል ጉዳይ ነው። ይሁንና ግን ከ29 ዐመት በኋላ ከሰማንያዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ የዓለም ህዝብ ወደብልጽግናና ተከታታይነት ወዳለው ሰላም ሊያመራ አልቻለም። ባለፉት 25 ዓመታት ከይጎዝላቢያ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ፣ አፍጋኒስታንና ኢራክ፣ እንዲሁም ሊቢያና ሶርያ በውጭ ኃሎች በተጠነሰሰ ጦርነት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህዝቦች ተገድለዋል። እንደዚሁም ቁጥራቸው የማይታወቁ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አካለ-ስንኩል ሆነዋል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተገደዋል። በየአገሩ የጥንት ታሪካዊ ከተማዎችና ቅርጾች እንዲወድሙ ተደርገዋል። ለመሆኑ የእነዚህ ሁሉ ምክንያት ምንድነው? ለምንድነው በየአገሮች ውስጥ እኩልነት የሰፈነበት ስርዓት ሊሰፍን ያልቻለው ?  በምን ምክንያትስ ነው በተሟላ የካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ በሚገኙ እንደፈረንሳይ፣ ጣሊያንና አሜሪካ በመሳሰሉት አገራት ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊፈጠር የቻለው ?

ይህ ጸሀፊ በየአገሮች ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ለመዳሰስ አይቃጣም። ከአቅሙ በላይ ስለሆነ በአጠቃላይ ነገሮች ላይ ብቻ በማትኮር አንዳንድ ነገሮችን ለመዳሰስ ይሞክራል። ስለሆነም ሀተታው አጠቃላይ በሆነ ነገር ላይ ቢያተኩር ምናልባትም እንዳልተሟላ አቀራረብ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በሌላ ወገን ግን አንዳንዶች በአሁኑ ጊዜ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ወዴት እንደሚያመራ በግልጽ በማይታወቅበት ወቅት ለምን በአጠቃላይ ነገር ላይ ማትኮሩ አስፈለገ ? ብለው ሊጠይቁ ይችሉ ይሆናል። በዚህ ጸሀፊ ዕምነት እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ ያለፈበት የታሪክ ውጣ ውረድና የማህበረሰብ አወቃቀር ቢኖረውም  በተለይም በአሁኑ በግሎባላይዜሽን ዘመን ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ፖለቲካዊ ድርጊቶች ዓለም አቀፋዊ ባህርይ አላቸው። ይህም ማለት ፖለቲካ በድርጊት ከመተርጎሙ በፊት በሃሳብ ደረጃ ከሳይንስ አንፃር የሚውጠነጠን እንደመሆኑ መጠን በየአገሮቹ ውስጥ የሚካሂደው ፖለቲካ የቱን ያህል በፍልስፍና ላይ ነው የተመሰረተ የሚለው ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ይኖረዋል ማለት ነው። በተጨማሪም ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ይዞ ከመጣ ወዲህ በምርት፣ በፍጆታ አጠቃቀም፣ በንግድ ትስስርና በዕዳ አማካይነት በብዙ አገሮች ውስጥ ሰርጎ በመግባት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በብዙ አገሮች የፖለቲካ መድረክ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር ችሏል። ከዚህም ባሻገር የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የመንግስት መኪና ከካፒታሊስቱ ዓለም ጋር በብዙ ሺህ ድሮች የተሳሰረ በመሆኑ በየአገሮች ፖሊሲ ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያሳድራል። ይህም ማለት የየአገሮች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ሁኔታዎች በራሳችን የማሰብ ኃይልና ድርጊት ብቻ የሚወሰኑ አይደሉም። እንዲያውም በአማዛኝ ጎኑ የውጭው ተፅዕኖ ለዕድገታችን እንቅፋት በመሆን ህብረተሰብአዊ መዘበራረቅን አስከትሏል። ከዚህ ስንነሳ ከአጠቃላይ ሁኔታ ተነስተን ወደ ተናጠል ነገሮች መምጣቱና ለመተንተን መሞከሩ ሳይንሳዊ አካሄድ ነው ማለት ይቻላል።

በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ አስፈላጊነት !

ስለ ፖለቲካ ሲወራ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ ከማደራጀትና በስነ-ስርዓት እንዲኖር ከማድረግ ጋር የሚያያዝ ፅንሰ-ሃሳብ ነው። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ አነሰም በዛም ካለብዙ ውጣ ውረድ ወይም ግብግብ ከአንድ ትውልድ ወደ ሚቀጥለው እንዲሸጋገር ከተፈለገ ፖለቲካና ፖለቲካዊ አደረጃጀት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። አንድ ማህበረሰብ በስነ-ስርዓት እንዲደራጅ ከተፈለገ ደግሞ ፖለቲካ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የግዴታ ከፍልስፍና ጋር መያያዝ አለበት። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ወይም ማህበረሰብ ከየት እንደመጣ፣ በዚህች ዓለም ላይ ለምን እንደሚኖርና ወዴትስ እንደሚያመራ ሊገነዘብ ወይም ሊረዳ የሚችለው ማህበረሰቡም ሆነ ፖለቲካን የሚቆጣጠረው የገዢ ኃይል ፍልስፍናን መመሪያቸው ማድረግ የቻሉ እንደሆነ ብቻ ነው። ፍልስፍናዊ ህይወት ደግሞ የግዴታ የኑሮን ትርጉም እንድንረዳ፣ ህይወታችንን እንድናሻሻል የሚረዳን፣ ማድረግ በሚገባንና በማይገባን ነገር ላይ ያለውን ልዩነት በሚገባ እንድንገነዘብ የሚረዳን ነው። ስለዚህም ነው እነፕላቶናን የተቀሩት ታላላቅ ፈላስፋዎች ፖለቲካን ከፍልስፍና ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩትና የሞራልንም ጥያቄ አጥበቀው ያነሱት። በሌላ አነጋገር ፖለቲካ በፍልስፍናና በሞራል ላይ ተመስርቶ የማይቀየስ ከሆነ አንድን ህብረተሰብ ወደ ማይፈልገው አቅጣጫ እንዲጓዝ ነው የሚያደርገው። ስለሆነም በተለይም ታዳጊ ትውልድ መመሪያ የሚሆነውን የሞራል ኮምፓስ ስለሚያጣ ታሪክን ከመስራት ይልቅ በአልባሌ ቦታውች እንዲውል ይገደዳል።

ትላንትም ሆነ ዛሬ በብዙ የሶስተኛው ዓለምም ሆነ በአንዳንድ የካፒታሊስት አገሮች- እንደ አሜሪካ በመሳሰሉት- የሰፈነውንና ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታየውና በስልጣን መባለግ ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ ያሉ ሀብቶች የሚወድሙት ስልጣንን የሚቀዳጁ ወይም የሚጨብጡ ኃይሎች አንዳች የሚመሩበት ፍልስፍና ስለሌላቸው ነው። በብዙ የሶስተኛው  ዓለም አገሮችና በአገራችንም ጭምር ሲወርድ ሲዋረድ በተከታታይነት የዳበረ በፍልስፍና ላይ የተመረኮዘ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ህብረተሰብአዊ ትችት የሚታወቅ ባለመሆናቸው በአጠቃላይ ሲታይ አገዛዞችም ሆነ ህዝቦች ለምን እንደሚኖሩና ወዴትስ እንደሚያመሩ አያውቁም ማለት ይቻላል። በተለይም በመንግስት ግልበጣ ወይም ደግሞ በምርጫ ስልጣንን የሚጨብጡ ኃይሎች አብዛኛውን ጊዜ የመንግስትን መኪናን ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ የየአገሮቻቸውን ሀብት የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው አድርገው በመቁጠር ሀብት ከማውደም ባሻገር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋሉ። በበሽታ እንዲጠቁ ይሆናሉ። በአገራቸው ውስጥ ተከብረው ለመኖር ስለማይችሉ የተሻለ ዕድል ለማግኘት ሲሉ በረሃንና ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካና እንዲሁም ወደተቀረው ዓለም እንዲሰደዱ ይገደዳሉ።

እንደሚታወቀው በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ምሁራዊ እንቅስቃሴዎችና ውይይቶች እንዲሁም ክርክሮች የተለመዱ አይደሉም። በተለይም በአገራችን ምድር ዲግሪ ያገኘ ወይም የጨበጠ ሁሉ የተማረ የሚመስላቸው አሉ። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ከፍተኛ ስህተት ነው። በእርግጥ አብዛኛው ህዝብ አንድ ሰው ዲግሪ መጨበጡን ነው እንጂ የሚያየው በዲግሪው አዲስ ህብረተሰብ ይመስርት ወይም አይመስርት፥ ቴክኖሎጂን ያዳብር ወይም አያዳብር፣ ሁለንታዊና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ሊያመጣ ይችላል ወይም አይችልም ብሎ የሚጠይቅ የለም። የተማረው ራሱም የራሱን ኑሮ ከማሻሻልና ተገልሎ ከመኖር በስተቀር በህብረተሰብ ውስጥ የሚያመጣው ለውጥ የለም። እንዲያውም  በአብዛኛው ጎኑ ተማረ የሚባለው ኃይል ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር ሀብት እንዲዘረፍ ያደርጋል። ከውጭ ምክር በመቀበል ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከተስተካከለ ዕድገት ይልቅ የባሰውኑ ፀረ-ዕድገትንና መዝረክረክን ነው  የሚያስከትለው። ለዚህም ነው በተለይም ዘመናዊ ትምህርት የሚባለውና መንፈስን ለማደስ የማይችለው ፀረ-ዕድገት የሚሆነውና ለህብረተሰብ ውዝግብ አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥረው።

ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ ? እንዴትስ በድፍረት እንደዚህ ብለህ ትጽፋለህ ? ብለው አንዳንዶች ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችሉ ይሆናል። በዕውቀት ዙሪያ ለሶስት ሺህ ዐመት ያህል የተደረገውን ክርክር ለተከታተለና፣ በተጨማሪም በካፒታሊስት አገሮችና በሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለውን የአኗኗር ሁኔታ እያነፃፀረ ቢመለከት በቀላሉ መልስ ሊያገኝ ይችላል። ማነፃፀር ለማይችለው ደግሞ በአገራችንና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለውን የኑሮ ሁኔታ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂን አለማደግ ጉዳይ እንደ ተፈጥሮአዊ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል። ያም ሆነ ይህ በዕውቀት ዓለም ውስጥ አንድ ነገር ከሌሎች ነገሮች ጋር የተያያዘ መሆኑንና በጥልቀትም የሚታይና የሚመረመር በአንድ በኩል፣ በሌላው ወገን ደግሞ በነገሮች መሀከል መያያዝ እንደሌላና አንድም ነገር በጥልቀት መታየት የለበትም በሚለው የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ከእነፕላቶን ጀምሮ እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የጦፈ ክርክር ተደርጓል። በተጨማሪም ዕውቀት የሚባለው ነገር እንዴት ነው ሊመነጭ የሚለው በፈላስፎች ዘንድ ሲያከራክር ነበር። እነፕላቶን ዕውቀት በቀጥታ ከምናየው ነገር ላይ የሚመነጭ ሳይሆን ከሱ ባሻገር ያለና በከፍተኛ የጭንቅላት ስራ የሚገኝ ነው ሲሉ፣ እነ አርስቲቶለስ ደግሞ ዕውቀት በቀጥታ ከሚታይ ነገር እንደሚፈልቅ ይነግረናል።  ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ ከ19ኛው ከፍል-ዘመን ወዲህና በተለይም ሶሻል ሳይንስ የሚባለውና የኢኮኖሚክስ ትምህርትንም ጭምሮ ከዕድገት ጋር፣ በተለይም ከፍልስፍና፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር ግኑኝነት የላቸውም ተብሎ በየትምህርትቤቱና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ ስለሚደረግ ወይም በስርዓት ስለማይሰጥ ይህ ዐይነቱ የትምህርት አሰጣጥ ዕውነት የመሰላቸው በማስተጋባት እንደምናየው በብዙ አገሮች ውስጥ ዕውነተኛ የሆነ ምሁራዊ ኃይል ሊዳብር አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድን ህዝብ የሚጠቅም የተስተካከለና ረጋ ያለ ሁለ-ገብ ዕድገት ሊመጣ አልቻለም።

ከዚህ ስንነሳ በየአገሮች ውስጥ ስልጣንን የሚጨብጡ ኃይሎች የዚህ ዐይነቱ አንድን ህብረተሰብ በስነስርዓት ለማደራጀት የማይችል የትምህርት ስርዓት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲከኛ የሚባሉ አስተሳሰባቸው የጠበበ ስለሚሆን ወይም ወደተለያየ አቅጣጫና ወደ ውስጥ ለመመልከት ስለማይችሉ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት እንዳላቸው አይገነዘቡም። ፖለቲካን የሚረዱት ራሳቸውን ማደለቢያ መሳሪያ አድርገው እንጂ በፖለቲካ አማካይነት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዴት እንደሚፈጠር፣ ከተማዎች እንዴት በስርዓት እንደሚገነቡ፣ ቴክኖሎጂና ሳይንስ እንዴት እንደሚዳብሩና ጥቅም ላይ እንደሚውሉ፣ ህብረተሰቡም በየረድፉ እንዴት እንደሚደራጅና መብቱን አስጠብቆና ራሱም ህግና ስርዓትን ጠብቆ እንዴት ተሳስቦ እንደሚኖር አይደለም ፖለቲካን የሚገነዘቡት።

በአገራችን ምድር አሁንም ቢሆን ያለው ትልቁ ስህተት ስለ አንድ ፓርቲ አገዛዝ፣ ስለአምባገነንነትና ምርጫ ስላለመኖር ወይም በፓርቲዎች መሀክል ተወዳዳሪነት አለመኖር ሲወራ የሚዘነጋው ነገር የአገራችንም ሆነ የአብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ችግር እነዚህ ሳይሆኑ የመንፈስ ነፃነት አለመኖር ነው። በሌላ አነጋገር ስልጣንን የሚጨብጡ ወይም የጨበጡና መጨበት አለብን ብለው የሚታገሉ ኃይሎች በሙሉ የመንፈስ ወይም የጭንቅላት ተሃድሶ ያላደረጉ ናቸው። ጭንቅላታቸውም በፍልስፍና የታነፀ ስላልሆነ ስለ ሰው ልጅም  ሆነ ስለ አጠቃላዩ ዕድገት የሚያውቁት ነገር የለም። አብዛኛውን ጊዜ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ አፍሪካ አገሮች ውስጥ  ስለ ዕድገት ያለው ግንዛቤ ንግድን ማስፋፋት ብቻ ወይም ደግሞ በሽቀላ ዓለም ውስጥ መሽከርከርን ነው። አብዛኛዎች የአፍሪካ አገዛዞችም ሆነ ከውጭ ሆነው መቼ ነው ስልጣን ላይ የምንወጣው ብለው እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱ ወይም በውጭ ኃይል የሚጠመዘዙ ኃይሎች ለአንድ አገር ዕድገት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ሚና በፍጹም አይረዱም። ከዚህም ባሻገር በተለያየ የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ መሀከል ያለውን ልዩነት ስለማይገነዘቡ አንድ ቀን በአጋጣሚ ስልጣን በሚጨብጡበት ጊዜ ተዓምር የሚሰሩ ይመስላቸዋል። ሀቁ ግን የፈለገው ኃይል ስልጣንን ይጨብጥ ራሱን በፍልስፍና ካላነጸ በስተቀር የዓለም ኮሙኒቲው፣ ወይም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚያቀርቡለትን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ አገሩን የባሰ ያዝረከርካል፣ ህዝቡንም የባሰውኑ ደሃ ያደርጋል።

በዚህ ምክንያት የተነሳ በብዙ የአፍሪካ አገሮች፣ አገራችንም ጨምሮ የሃማኖትና የብሄረሰብ ግጭቶች አሉ። ለእንደነዚህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ አለመረጋጋት ዋናው ችግር በመሰረቱ ፖለቲካዊ አወቃቀሩ በፍልስፍና ላይ ባለመመስረቱና ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የፖለቲካን ትርጉም በደንብ ስለማይረዱ ነው። እንደኛ ባለው አገር ደግሞ ፖለቲካ ወደ ተንኮል፣ ወደ ሽወዳ፣ ወደ መከፋፈልና መለያየት በመለወጥ ወይም በመተርጎም ህብረተሰቡ በዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ እንዲኖር ይደረጋል። ሃሳቡ በአየር ላይ በመንጠልጠል የሚሰራውን ስለማያውቅ በአንዳንድ በዞረባቸው ኃይሎች በመቀስቀስ በሌላው በሱ መሰል ወንድሙ ወይም እህቱ ላይ እንዲነሳ ይደረጋል። የአገራችንን የ27 ዐመት የወያኔን ፖለቲካ ስንመለከት በዚህ ዐይነቱ የተንኮልና የሽወዳ እንዲሁም የከፋፍለህ ግዛ „ፍልስፍና“  ላይ የተመረኮዘ ነበር። ይህንን ያደርግ የነበረው ለዝንተ-ዓለም አገራችንን ለመግዛትና ህዝባችንን አደንቁሮ ለማስቀረት በማሰብ ብቻ ነበር። በተለይም ህዝባችን ርስበርሱ እንዲጨራረስ ያላደረገውና ያልሸረበው ሴራ አልነበረም። ለዚህ እርኩስ ተግባሩ ደግሞ የእንግሊዝ የስለላ ድርጅት፣ ሞሳድ፣ የጀርመን የስለላ ደርጅትና ሚሺነሪዎች ፣ እንዲሁም በእርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በአገራችን ምድር የሶርያ ዐይነት ሁኔታ እንዲፈጠር የማያደርጉት እርክሱ ተግባር የለም። በሲአይ ኤና በሌሎች የስለላ ድርጅቶች የስለጠኑ ኢትዮጵያኖችም የዚህ ዐይነቱ እርኩስ ስራ ተባባሪዎች ናቸው። ከዚህ ስንነሳ ወያኔ ወይም ትግሬዎችና ኤርትራውያን ብቻ ሳይሆኑ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡና ለሆዳቸው ያደሩ ኢትዮጵያውያን በአገራችን ምድር የእርስ በእርስ መተላለቅ እንዲመጣ የማያደርጉት እርኩስ ስራ የለም። የምንለምናቸው ነገር ቢኖር ከእንደዚህ ዐይነቱ አገርን ከሚያጠፋና ህዝብን ከሚያስጨርስ እርኩስ ተግባር ተቆጠቡ ብቻ ነው የምንላቸው። እባካቸሁ ልብ ግዙ፣ ራሳችሁንም ጠይቁ ብለን ነው የምንማፀናቸው። በታሪክና በህዝብ ላይ ወንጀል አትፈጽሙ እያልን ነው ከእግራቸው ስር ወድቀን የምንለምናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲ ነን ወደሚሉት ጋ ስንመጣ የምናየው ችግር አገርቤትም ሆነ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በውጭ አገር እንቀሳቀሳለን እንቀሳቀሳለን ይሉ የነበሩትን „ድርጅቶች“ ጨምሮ አንዳች ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍና የላቸውም። ለምን ዐይነትስ ህብረተሰብና እንዴትስ ጠንካራ ኢትዮጵያን እንደሚገነቡ እስካሁን ድረስ የነገሩን ነገር የለም። በጽሁፍም ደረጃ በደረጃ እየተነተኑ አላስረዱንም። ሁሉም ስለምርጫና ውድድር፣ ስለመደብለ ፓርቲ መኖር፣ አሁን ደግሞ ስለ ሽግግር መንግስትና ስለሽግግረ-ዲሞክራሲና፣ ከዚያም በላይ ስለሊበራል ዲሞክራሲ አስፈላጊነት ነው የሚያወሩት እንጂ እንዴት አድርገው የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች እንፈታለን ብለው አይደለም። በተለይም አብዛኛዎች ስለሊበራል ዲሞክራሲ አስፈላጊነት ቢስማሙም ይህ ፅንሰ-ሃሳብ ምን ማለትና በዚህ አማካይነት እንዴት ተደርጎ ሰፋ ያለና የጠነከረ፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ እንደሚገነባና ህዝባችንም የዚህ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሲያስተምሩን አይታዩም። በእኔ ዕምነት በተለያዩ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ነን በሚሉት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሃሳብ መዘበራረቅ ያለ ነው የሚመስለኝ። ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትም ያላቸው ግንዛቤ ግልጽ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚ የሚባለውን ፅንሰ-ሃሳብ ከኢኮኖሚ ዕድገትና ከህብረተሰብ ግንባታ ለይተው ነው የሚያዩት። በመሆኑም በዚህ ላይ አንዳች ግንዛቤ እስከሌለ ድረስ ስለ ሽግግር መንግስት፣ ስለሽግግር ዲሞክራሲና ስለመሰረታዊ ለውጥ ማውራት በፍጹም አይቻልም ማለት ነው።

በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ዕውቀት የአንድን አገር ችግር ለመረዳት ያስችላል !

አንድ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ አገራችን መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋታል ሲል ለምን መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ማሳየት አለበት። እንደገባኝ ከሆነ የአብዛኛዎቻችን መሰረታዊ ለውጥ ፍላጎት ከፖለቲካ ስልጣን ተሻግሮ የሚሄድ አይደለም። የአብዛኛዎቹ ምኞት እንዴት አድርገን ስልጣን ላይ እንወጣለን ብለው የሚታገሉ እንጂ በምን ዘዴና የፖለቲካ ስትራቴጂ አገራችንን አሁን ካለችበት ሁኔታ እናወጣታለን? በማለት አይደለም እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱት።

ይህንን ትተን ወደ ተወሳሰበው የአገራችን ችግር ስንመጣ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። አንደኛውንና አስቸጋሪውን ነገር ከላይ በመጠኑም ቢሆን ለመጠቆም ሞክሪያለሁ። ይኸውም በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠር የፖለቲካ ውዝግብና በሀብት መደለብ የግዴታ ከጭንቅላት ድህነት ጋር የተያያዘ ነው የሚል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማንበብ ችግር አለ። አብዛኛዎች ክስተታዊ በሆነ ዕውቀት የተገነባን ስለሆነ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖረውን ተጨባጭ ሁኔታን ለማንበብ ችግር አለብን። አንድን ተጨባኝ ሁኔታ ለማንበብ ደግሞ ይዘታዊ የሆነ ምርምርና(qualitative) በቁጥር የሚለካ ወይም ኢምፔሪካል የሚባል የምርምር ዘዴ አለ። አብዛኛውን ጊዜ ኢምፔሪካል ጥናት በትናንሽ ነገሮች ላይ ስለሚያተኩር አጠቃላይና ስር የሰደደን የአንድን ህብረተሰብ የተወሳሰበ ችግር እንድንመረምርና እንድንረዳ አያግዘንም። ስለሆነም ኢምፔሪካል ጥናት ወደ ተፈለገው መፍትሄና ህብረተሰብ ግንባታ ላይ እንድናተኩር የሚረዳን አይደለም።

ስለሆነም ይዘታዊ(qualitative) ጥናትና ምርምር የአንድን ህብረተሰብ ችግር ለመረዳት ይረዳናል። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር የኢኮኖሚ ግኑኝነትና የፖለቲካ አወቃቀር ነፀብራቆች(manifestations)በግልጽ ይታያሉ። እነዚህም ድህነት፣ ረሃብ፣ የስራ-አጥነት፣ እጅግ ተጎሳቅሎ መኖር፣ የከተማዎች መዝረክረክ ወይም በስርዓት አለመገንባት፣ በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ህዝብ ሊኖርባት የሚችልባትን አገር ጥበባዊ በሆነ መልክ ለመገንባት አለመቻል… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የተበላሸና ፍልስፍና አልባ ፖለቲካ ነፀብራቆች ናቸው። ፖለቲካዊ አወቃቀሩና የመንግስት መኪና፣ እንዲሁም አጠቃላዩ የትምህርት አሰጣጥ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በመጣስ የተመሰረቱ ስለሆነ፣ ችግርን ፈቺዎች ከመሆን ይልቅ ችግርን ፈጣሪዎችና እየተወሳሰቡ እንዲሄዱ የሚያደርጉ ናቸው።

ከአንድ ዓመት  በፊት የዶ/ር አቢይን መመረጥ አስመልክቶ ባወጣሁት ጽሁፍ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ባለፉት 27 ዐመታት በአገራችን ምድር ውስጥ አዲስ ዐይነት የህብረተሰብ አወቃቀርና የምርት ግኑኝነት ተፈጥሯል። ይህም ማለት በአገራችን ምድር ከፖለቲካው አወቃቀር ባሻገር ስትራቴጂክ የሆኑ የምርትና የግልጋሎት መስኮችን የሚቆጣጠር የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ብሏል። ይህ ዐይነቱ የምርት ግኑኝነት ደግሞ ከፖለቲካውና ከመንግስት መኪና ጋር የተቆላለፈ በመሆኑ ለአገሪቱ ዕድገት ከፍተኛ ማነቆ ሆኗል ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ በፖለቲካው፣ በመንግስት መኪናና በኢኮኖሚው መሀከል መቆላለፍ እስካለ ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ግልጽ የሆነ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመረኮዘና አዳዲስ አምራች ኃይሎችን የሚያፈልቅ የህብረተሰብ ኃይል ማፍለቅ አይቻልም። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ የ 27 ዐመቱን የወያኔን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለተመለከተ ለትናንሽና ለማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንደ አሸን መፍለቅ የሚያመች አልነበረም; አይደለምም። በተከተለው በኒዎ-ሊበራልዝም ላይ በተመረኮዘ የሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት አብዛኛውን ነጋዴና አምራች ኃይል በአገልግሎት መስክ ላይ እንዲሰማራ ነው ያደረገው። እንደሚታወቀው ደግሞ ይህ ዐይነቱ በአንድ የኢኮኖሚ መስክ ላይ ያዘነበለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሰፋ ያለ ሀብት ሊፈጥር የማይችል በመሆኑ አብዛኛው ህዝብ በስራ-አጥነት ይሰቃያል። ከዚህም ባሻገር የጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ እዚህና እዚያ ተዝረክርከው የሚገኙ የችርቻሮ ንግዶች፣ በግልጽ ያልተደራጀ የአመአራረት ስልትና አገልግሎት(Informal Sector) እነዚህ ነገሮች ግልጽ ለሆነ ስራ-ክፍፍልና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ ሰፋ ላለ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋቶች ናቸው። ከዚህም ባሻገር አገራችን የቆሻሻ ዕቃዎች(Second Hand Goods) መጣያ በመሆኗ ይህ በራሱ ለጠራና ግልጽ ለሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እንቅፋት ነው ማለት ይቻላል።\

ወደ እርሻው መስክ ስንመጣ ደግሞ መሬትን ለውጭ ከበርቴዎች በማከራየት አበባ እንዲተከል ማድረግ፣ ለውጭ ገበያ በሚውሉ ሰብሎች ላይ መሰማራትና የሸንኮራ አደጋን መትከልና ማስፋፋት በከፍተኛ ደረጃ የገጠሩ መሬት በስነ-ስርዓት እንዳይታረስና የሀብት መሰረት እንዳይሆን ተደርጓል። አብዛኛው ገበሬ ከመሬቱ በመፈናቀል ወደ ተራ ሰራተኛነት ተቀይሯል። ስራ ለማግኘት የማይችለው ደግሞ ወደ ከተማዎች በመሰደድ በአልባሌ ስራዎች ላይ ተሰማርቷል። በአጠቃላይ ሲታይ ይህ ዐይነቱ የአንድን አገር ሀብት በስነስርዓት ለመጠቀም እንዳይቻል የህውሃት አገዛዝ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የፈጠረው አዲስ የኢኮኖሚ ግኑኝነት በራሱ ለጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ነው። ከዚህ ባሻገር አላሙዲና አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች የአገሪቱን ሀብት እንዲዘርፉ የተሰጣቸው የወርቅና የሌሎች ዕንቁ የሆኑ ጉድጓዶች አገሪቱን ከማራቆት ባሻገር፣ አካባቢውን በመርዝ እየበከሉና የሚወለደውንም ህፃን አካለ ስንኩል እንዲሆን እያደረጉ ናቸው። እነዚህንና እጅግ የረቀቁና በግልጽ የማይታዩ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግኑኝነቶችን መመርመርና መፍትሄም መስጠት የምንችለው በፍልስፍናና በሶስዮሎጂ ላይ በቂ ግንዛቤ ሲኖረን ብቻ ነው። በፍልስፍና መነፅር ብቻ ነው የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር በመረዳት ሳይንሳዊ መፍትሄ መስጠት የምንችለው። ከዚህ በመነሳት ለምንድነው ለፖለቲካዊ ለውጥ የምንታገለው ? በሚለው ላይ ላምራ።

ለምንድን ነው ለፖለቲካ የምንታገለው ?

እስከዛሬ ድረስ በፖለቲካ የህይወት ታሪኬ ውስጥ ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር ለምን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ህይወቱን እንዳጣ ነው? ከጦርነት ትግል በስተቀር ሌሎች አማራጭ የትግል ዘዴዎች የሉም ወይ ? እነዚህና ሌሎች ከአመጽ ጋር የተያያዙ ትግል የሚባሉ ፈሊጦች በአማዛኝ ጎናቸው ወደ ተፈለገው ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳላመሩ በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች በነፃነት ስም የተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ ያረጋግጣሉ።

በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ አንድም ጊዜ የየአገሬው ሰፊ ህዝብ ለጦርነት ምክንያት ሆኖ አያውቅም። ለዲሞክራሲና ለነፃነት እንታገላለን ብለው በከተማም ሆነ ወደ ጫካ ገብተው የጦር ትግል የሚያካሂዱ ኃይሎች በትንሹም ሆነ ወይም በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ሰዎች ናቸው። በየአገሩ ባሉ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ያገባናል በሚሉ ኃይሎች አማካይነት አንድ ቦታ ላይ የተቀሰቀሰው ትግል እየተቀጣጠለ በመሄድ ወደ አጠቃላይ ጦርነት ያመራል። ጦርነቱ ክልላዊ ከመሆን አልፎ ወደ አገራዊነት በመሸጋገር ያለተመጣጠነ ኃይል ባላቸው በአንድ በኩል በመንግስት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የነፃነትንና የዲሞክራሲን ጥያቄ አንግበው በሚነሱ ኃይሎች መሀከል ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ዐይነቱ አንድ ቦታ ላይ የተቀሰቀሰ ጦርነት በመጀመሪያ እንደታለመውና እንደሚመኙት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑ ቀርቶ ሰላሳና አርባ ዐመታት የሚፈጅ ይሆናል። በዚህ መልክ የሚካሄደው ጦርነት የራሱን የውስጠ-ኃይል(Dynamism) በማግኘት ከመንፈሳዊ ባህርይ በመላቀቅና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል  መሆኑ ቀርቶ ሙሉ በሙሉ በጦርነትና በማሸነፍ ሎጂክ ስለሚሸፈን ከድል በኋላ ሊደረጉ ወይም ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮች ይረሳሉ። በዚህም ምክንያት የጦር ትግልን የጀመረ ነፃ አውጭ ነኝ የሚል ኃይል ራሱ በድል አድራጊነት ስልጣንን ሲጨብጥ ነፃነትንና ዲሞክራሲን አምጭ ወይም አራማጅ መሆኑ ቀርቶ ወደ በዝባዥነትና ወደ አገር አፍራሽነት ይለወጣል።  በመጀመሪያ የታቀደው ለእኩልነት የሚደረገው ትግል አቅጣጫውን በመቀየር ወይም ወደጠባብነት በመለወጥ አዲስ ዐይነት ጭቆናን የሚያሰፍንና የስልጣኔን ናፍቆት የሚያረዝም ስርዓት ይፈጠራል ማለት ነው።

በላፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት በተለያዩ አገሮች በተለይም በአፍሪካ ምድርና በአገራችንም ጭምር በነፃነት ስም የተካሄዱትን እልክ አስጨራሽ ጦርነቶችን ስንመለከት የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ብርሃን ከማምራት ይልቅ ወደ ጨለማነት ሊያመሩ የቻሉት በመጀመሪያውኑ ሙሉ በሙሉ በጦርነት ሎጂክ ስለሚሸፈኑና በመሪዎችም ጭንቅላት ውስጥ ጦርነት ማካሄድና ማሸነፍ አስተሳሰብን ቆልፈው ስለሚይዙ ነው። በተወሳሰበ መልክና በእልክ የሚካሄድ የጦር ትግል የመጨረሻ መጨረሻ የሰውን አርቆ የማሰብ ኃይል ክፍል ስለሚይዘው፣ ሌሎች ከማሰብ ኃይል ጋር ተቆላለፈው የሚገኙ በተለያየ መልክ የሚገለጹ ስሜት ነገሮች በሙሉ ደብዛቸው እንዲጠፋ ይደረጋል። በዚህ መልክ በኃይል የፖለቲካ ስልጣንን የሚጨበጡ የተደራጁ ኃይሎች ከዕውነተኛው የነፃነትና የዲሞክራሲ መርህ በመራቅ የራሳቸውን አዲስ ዓለም ይፈጥራሉ። በተለይም የመንግስት የመጨቆኛ መሳሪያዎችን በማጠናከር በአንድ ሰሞን ለዲሞክራሲና ለነፃነት እንታገላለን ብለው የተነሱ ኃይሎች ጨቋኝና በዝባዥ ይሆናሉ። በራሳቸው ዓለምም ስለሚኖሩ ስርዓት ያለው ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸው መልሰው ፀረ-እኩልነትን ያሰፍናሉ። ይህ ሁኔታ በራሱ ለሌላ የጦርነት ትግል የሚጋብዝ ይሆናል።

ይህ ዐይነቱ ችግር የሚመነጨው በመሰረቱ የፖለቲካ ዓላማን ከመጀመሪያው በደንብ ካለማውጠንጠን የተነሳና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የኃይል አሰላለፍና የሚኖረውን ተፅዕኖ  በሚገባ ካለማጥናት ነው። ከመጀመሪያውኑ ፖለቲካ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ውይይታዊ በሆነና በክርክር መልክ ጥያቄ በማንሳትና ለመመለስ በመሞከር የሚገለጽ መሆኑ ቀርቶ ስልጣን ከመጨበጥ ጋር የሚያያዝ ስለሚሆን አቅጣጫን በመሳት የተፈለገውን ዓለማ ለመምታት የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሰረቱ ፖለቲካ ከሌሎች ነገሮች ተለይቶ የሚታይ ነገር አይደለም። ፖለቲካ አንድ አገር የሚገለጽበት ሳይንሳዊ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን በአንድ የታሪክ ወቅት የሚኖርን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የተከታታይ ትውልድንም ህይወት የሚያካትትና የሚወስን ነው። በአንድ የታሪክ ወቅት በሁለንታዊ መልክ በውይይትና በክርክር ላይ ተመስርቶ ግልጽ ባልሆነ መልክ የሚካሄድ ፖለቲካ የአንድን አገርና የአንድን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የተከታታዩንም ትውልድ ህይወት አሉታዊ በሆነ መልክ የመቅረጽ ኃይል አለው። በሌላ በኩል ግን ከመጀመሪያውኑ የፖለቲካ ትርጉም ከዕውነተኛ የጭንቅላት ነፃነት ጋር ተያይዞ ሁለንታዊ በሆነ መልክ የሚገለጽ ወይም የሚተነተን ከሆነ የአንድንና የተከታታዩን ትውልድ አስተሳሰብ አዎንታዊ በሆነ መልክ ሊቀርጽ ይችላል።

ከዚህ ስንነሳ አንድ ድርጅት ወይም ኃይል የፖለቲካ ትግል አካሂዳለው ብሎ ሲነሳ ከመጀመሪያውኑ ግልጽ ማድረግ ያለበት ጉዳዮች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲካ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ፣ ከህብረተሰብ፣ ከባህል፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ እነዚህን ለአንድ አገር ግንባታ የሚያገለግሉ መሰረተ-ሃሳቦችን የማያካትት ፖለቲካ ከመጀመሪያውኑ ይከሽፋል። ስለሆነም ፖለቲካን መሰረተ-ሃሳብ አድርጎ ለመታገል የሚነሳ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከመጀመሪያውኑ ራሱ የነፃነትን ትርጉም የተረዳና ጭንቅላቱንም ከማንኛውም ዕድገትን ከሚቀናቀኑ ነገሮች ያፀዳ መሆን አለበት።

በፈላስፋዎች ምርምርና ዕምነት እንደማንኛውም ህይወት እንዳለውና ከታቸ ወደላይ እንደሚያድግ ፍጡር ነገር ጭንቅላትም ሙሉ በሙሉ ነፃነትን ለመቀዳጀት የተወሰኑ የክንውን ደረጃዎችን ማለፍ አለበት። እንደየአገሩ የማቴርያል ሁኔታ፣ ማለትም የምርት ኃይሎች ማደግ፣ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ በተቀናጀ መልክ መገኘትና የአንድ ሰው የቤተሰብ ሁኔታና ሌሎችም በረቀቀ መልክ የማይታዩና፣ የሚጨበጡና የሚታዩ ነገሮች የአንድን ሰው አስተሳሰብ ሊቀርጹ ይችላሉ። ለነፃነት ያለውንም ፍላጎት ይወስናሉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ግን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አይመለከትም። በተለያየ ምክንያትና በቀላሉ ለመግለጽ በማይቻል ሁኔታ የተለያዩ ሰዎች በአንድ አካባቢ ቢወለዱምና ተመሳሳይ ሁኔታ ቢኖራቸውም የሁሉም አስተሳሰበ ተመሳሳይ ይሆናል ማለት አይደለም። አንዳንዱ ውስጣዊ የሆነ የነፃነት ፍልጎት ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ የነፃነትን ትርጉም ሊረዳ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ነገሮችን በሙሉ ጠባብ በሆነ መልክ ስለሚመለከትና ሁኔታዎችንም ከዚህ በመነሳት ስለሚተረጉም በአንድ አገር ውስጥ ጭቆና ቢኖርም ይህንን እንደተፈጥሮአዊ አድርጎ ይወስዳል። በዚህም መልክ የተወሰነ ራሱን የሚያስደስት የኑሮ ሁኔታ ካለው ይህንን ይጋሩኛል በማለት ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ያፍናል። በሌላ ወገን ግን ኢምፔሪካል በሆነ መልክ እንደተረጋገጠውና፣ የፈላስፋዎችን፣ የሳይንቲስቶችን፣ የድራማ ሰዎችንና የታላላቅ ሰዓሊዎችን የህይወት ታሪክ ገረፍ ገርፍ አድርጎ ላነበበ እነዚህን የመሳሰሉት ምሁራን ከልጅነታቸው ጀምረው ጭንቅላታቸው በትክክለኛ ዕውቀት እንዲኮተኮት በመደረጉ ለነፃነት ያላቸው ፍላጎት ከመንፈሳቸው ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም በእንደነዚህ ዐይነቱ ግለሰቦች ዕምነት ማንኛውም የሰው ልጅ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዲቀዳጅና ስልጣኔንም ተግባራዊ እንዲያደርግ ከተፈለገ የግዴታ ልክ አንድ አትክልት ጥሩ ፍሬ በዐይነትም  ሆነ በብዛት እንዲሰጥ  በደንብ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የሰው ልጅ ጭንቅላትም ከህፃንነቱ አንስቶ የግዴታ በትክክለኛ ዕውቀት መኮትኮት አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ፖለቲካ ሁለንታዊ የሆነ ባህርይ እንዳለውና ከብዙ ነገሮች ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ይገባል። አንድን ህብረተሰብ በፀና መሰረት ላይ ለመገንባት ይቻላል። በመሆኑም ፖለቲካን አንግበን ለመታገል ስንነሳ ትግላችን ከስሜት የራቀ መሆን አለበት። የራሳችንንም ሆነ የህብረተሰብአችንን ሁኔታ በደንብ መመርመር አለብን። ይህ ሲሆን ብቻ ትግላችን የቀና ይሆናል። ከአጉል ሽኩቻ የፀዳ ይሆናል። ከመጀመሪያውኑ ኃላፊነትን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ስለሚሆን ለስልጣን መስገብገብ ቦታ አይኖረውም ማለት ነው።

ፖለቲካና  የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ !    

ዛሬ በአብዛኛዎች የላቲን አሜሪካ፣ የማዕከለኛው አሜሪካና አፍሪካም ጭምር ያለውን የፖለቲካ ትርምስና ህብረተሰብአዊ አለመግባባት ስንመለከት በቀጥታ ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ጋር የተያያዘ ነው። የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎች በሙሉ አሜሪካን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ የተማሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለዕድገት የማያመች ትምህርት በመቅሰማቸው በየአገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ውዝግብ ሊፈጠር ችሏል። እንደብራዚልና ሜክሲኮ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ለከፍተኛ ትምህርት ተብሎ ሃርባርድና ሌሎች የኤሊቶች ዪኒቨርሲቲዎች የሚላኩ ተማሪዎች በሙሉ ከከፍተኛው የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ናቸው። ትምህርታቸውንም ጨርሰው ሲመጡ በቀጥታ ከፍተኛ ስልጣን ይሰጣቸዋል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያለፉትን የሰላሰ ዐመታት የፖለቲካ ሁኔታ ጠጋ ብለን ስንመለከት ያለው ውዝግብና የፖለቲካ ውንብድና በዚህ ዐይነት የአሜሪካን ርዕዮተ-ዓለም በሰለጠኑ ኃይሎች የሚካሄድና ህዝብን ያስመረረ ነው። በተለይም የብራዚል ህዝብ በአገሩ ውስጥ ስንትና ስንት የተትረፈረፈ ሀብት እያለ ህዝቡ መኖር ስላልቻለ የቻለው ፖርቱጋል በቀኒሳ እየተሰደደ እየመጣ ነው። ከማዕከለኛው አሜሪካም እየተሰደደ ወደ ታላቁ አሜሪካ የሚገባው የፖለቲካው መስክ ከፍልስፍና ጋር ባለመያያዙና የገዢ መደቦችና ፖሊሲ አውጭዎች ኃላፊነትና ተጠያቂነት ስለማይሰማቸው ነው።

ወደ አገራችንም ስንመጣ አብዛኛው ፖለቲካኛ ባይና ፖሊሲ አውጭ በአሜሪካን ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠነ በመሆኑ የሚያደላው ለራሱና ለአሜሪካ እንጂ አገሬን እንዴት አድርጌ አሳድጋለሁ ብሎ አይደለም የሚጨነቀው። ሰሞኑን በአንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ  በቀረበ ዘገባ መሰረት ሁለት ትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ በሆኑ፣  በድሮዋ የኮሞዲቲ ልውውጥ ዳይሬክተር በነበረችው በዶ/ር ኤሌኒ ገብረ-መድህንና፣ ለኧርንስትና ያንግ(Ernst and Young) ለተባለ ኮንስተሊንግ ካምፓኒ ተቀጥሮ በሚሰራው በአቶ ዘመድኩን ንጋቱ አማካይነት የአገራችን ሀብት እንዴት እንደተቸበቸበና  እንደሚቸበቸብ፣ የአገራችንም መሬት ወደ አበባ ተከላነት እንደተለወጠ ጥሩ ምሳሌ ነው። ዶ/ር ኤሌኒ በተለይም የቡና የልውውጥ ገበያ በማቋቋም የአገራችን ገበሬ በዚያው ቀጭጮ እንዲቀር አድርጋለች።  እንደነዚህ ዐይነቱ በኒዎ-ሊበራል የገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና የሰለጠኑና ሌሎችም የአገራችንን ሀብት በመዝረፍና በማዘረፍ በራሳቸው ዓለም ውስጥ በመኖር ከፍተኛ ወንጀል እየሰሩ ነው። በዚህ መልክ ሰልጥነው በመንግስት መኪናና በባንክ ውስጥ የተሰገሰጉትና እንደ አማካሪም ሆነው የሚሰሩ ሁሉ ዛሬ አገራችን ለወደቀችበት አሳፋሪ ሁኔታ ተጠያቂዎች ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ሁለ-ገብ የሆነና ጤናማ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት እንዲመጣ ከፈለግን በመንግስት መኪናና ወደፊት በሚቋቋሙት ኢንስቲቱሽኖች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩትንና በባንክ ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉ ሁሉ ከፍተኛ የሆነ የሳይኮሎጂ ምርምር እንዲደረግባቸው ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የውጭ ዜግነት ያለው ኢትዮጵያዊ ወደ ስልጣን አካባቢ ከመምጣቱ በፊት የህይወት ታሪኩ መጠናት አለበት። ካለበለዚያ እንደ ዩክሬይን፣ ብራዚልና አርጀንቲና እንዲሁም እንደተቀሩት የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች በዘለዓለማዊ ውዝግብና ድህነት ውስጥ እንድንኖር ነው የሚደረገው። ስለዚህም በፍልስፍና መነፅር ሁሉንም ማጥናትና መመርመር ግዴታዊ የአገር ዜግነት ነው። መልካም ግንዛቤ!!

 

                                                       fekadubekele@gmx.de