Social
የህንፃ አሰራርና ቅርጽ የሰውን መንፈስ በመጥፎም ሆነ በጥሩ መልክ
የመቅረጽ ኃይል አለው !
– የገበያ አዳራሽ ጋጋታ አንድን ህብረተሰብ ሊለውጥና የመንፈስ ተሃድሶ ሊያመጣለት አይችልም-
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ታህሳስ 10፣ 2018
ለተከበሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ !
ውድ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደምን ሰንብተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ አበባን የመሰለ ካለዕቅድ የተሰራና ውጥንቅጡ የወጣ ከተማን ማስተዳደርና ማስተካከል ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን፣ በጣም አስቸጋሪም እንደሆነ ይገባኛል። በትክክል እንደተገነዘቡትና እንደተከታተሉት የአዲስ አበባ ከተማ ዕቅደ-አልባ ሆኖ ማደግና መስፋፋት የጀመረው በተለይም ዘመናዊነት የሚባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ከ1950ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ነው። በጊዜው እንደሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መካሄድ የጀመሩት በአዲስ አበባ ከተማና በአካባቢው ነበር፤ አሁንም ነው። ሌሎች የክፍለ-ሀገራት፣ በአሁኑ መጠሪያ ደግሞ የክልል ዋና ከተማዎች እንደከተማና ልዩ ልዩ ነገሮች የሚካሄድባቸው ሆነው ባለመቆጠራቸው በጊዜው የነበረው የአፄው አስተዳደር አትኩሮው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአካባቢውና በክፍለ-ሀገር ዋና ከተማዎች የስራ ዕድል ለማግኘት የማይችለው ህዝብና፣ በተለይም አስራሁለተኛ ክፍልን የሚጨርሰው ወጣት ወደ አዲስ አበባ ነው የሚጎርፈው። ይህንን የህዝብ ፍልሰት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የመኖሪያ ቤቶችና የባህል ማዕከሎች ሊሰሩ ባለመቻላቸው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስርዓተ-አልባ የሆነ የቤት አሰራሮች እዚህና እዚያ ሊስፋፉ ችለዋል። በቁጥር እያደገ ለመጣው ህዝብም የመፀዳጃ ቦታዎች በሚገባ ባለመዘጋጀታቸው አንዳንድ ቦታዎች ወደ መፀዳጃነት ተለውጠዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰው አፍንጫውን እየሸፈነ እንዲንቀሳቀስ ተገዷል። ይህ ሁኔታ የሚያረጋግጠው በጊዜው የነበረው የአፄው አገዛዝና የከተማው አስተዳደር ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆነና፣ ዕውነተኛ የህዝብ ነፃነትና ፍላጎት በምን መልክ መሟላትና መገለጽ እንዳለባቸው የተገነዘቡ እንዳልነበሩ ነው። በተጨማሪም ከተማ መኖሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የባህል ማዕከልም እንደመሆኑ መጠን፣ ኗሪው ደስተኛ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም እንዲሆን ምን ምን ነገሮች በቅደም ተከተል መወሰድና፣ ከተማዎችም በምን መልክ መገንባት እንዳለባቸው የተረዱ አልነበሩም። ስለሆነም አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የክፍለ-ሃገራት ከተማዎች ሁሉ የሰው ልጅ እንዲኖርባቸው ሆነው በስርዓት ታቅደው የተሰሩ አልነበሩም።
የወታደሩ አገዛዝ ስልጣን ከያዘ በኋላ በጊዜው በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የተነሳ ፋታ ባለማግኘቱ የአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ መልክ ታቅዶ መገንባትና መስፋፋትም ሆነ ያለውን ማሻሻል ያስፈልጋል በሚለው ላይ ይህን ያህልም አትኩሮ አልተሰጠውም። በተለይም ጊዜው የአብዮት ዘመን ስለነበር ምሁሩም ሆነ የወታደሩ አገዛዝ አትኩሮአቸው አብዮት በሚለው አስተሳሰብና ስልጣንን እንዴት እንያዝ ብሎ እዚህና እዚያ ከመሯሯጥ በስተቀር አገራችንን በምን መልክ መገንባት አለብን፣ ከተማዎችም እንዴት መገንባት አለባቸው በሚሉት መሰረታዊ የአገር ጉዳዮችና የህዝብ ጥያቄዎች ላይ ምንም ዐይነት ውይይት አይካሄድም ነበር። በተለይም የከተማን ዕቅድንና የህንፃ አሰራርን በሚመለከት ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስለማይካሄድና፣ ባህልም ስለሌለ የሚሰሩት ስራዎች በሙሉ በአቦ ሰጡኝ ነው ማለት ይቻላል።
የህዋሃት አገዛዝ ስልጣንን ከጨበጠና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ስትራቴጂክ የኢኮኖሚ መስኮችን መቆጣጠር ከጀመረ ወዲህ የህዋሃት አባላትም ሆነ እሱን የተጠጉት ግለሰቦች ሆን ብለው የተያያዙት ከህዝባችን ፍላጎት ጋር ሊሄድ የሚችልና ለከተማዋ ውበት በመስጠት የፈጠራን ስራ ሊያዳብር በሚችል የህንፃ አሰራር ላይ ሳይሆን መረባረብ የጀመሩት፣ በመሰታወት የተሸፈኑ ትላልቅ ህንፃዎች እዚህና እዚያ መስራትና ትላልቅ ሆቴል ቤቶች እንዲሰሩ፣ ሊሰራ ይችላል ብለው ለገመቱት ደግሞ የመገንቢያ ፈቃድ በመስጠት ላይ ነበር ዋናው አትኩሮአቸው። ይህ ዐይነቱ የከተማ ቦታ ቅርምትና ካለዕቅድ እዚህና እዚያ ትላልቅ ህንፃዎችን መስራት በኗሪው የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ከፍተኛ መፈናቅልን ብቻ ሳይሆን የህሊና ውድቀትም ሊያስከትል እንደቻለ የምንገነዘበው ሀቅ ነው። የዚህ ዐይነቱ የህንፃ አሰራር ክስተት በየቦታው የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች(Slums) እንድ አሸን መፍለቅ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ቦታዎች ልዩ ልዩ ባህልን የሚያበላሹ ነገሮች መፈልፈያ ሊሆኑ በቅተዋል ማለት ይቻላል። ባህልን፣ ታሪክንና የህዝብን ፍላጎት በማካተት ከረጅም ጊዜ አንፃር በማሰብ ከተማዎችን፣ በክፍል በክፍል እየለዩ የመኖሪያ ቦታዎችን፣ የባህል ሰፈር፣ የስፖርት ክንዋኔ ቦታዎችን፣ የመደብሮችና የገበያ አዳራሽ ቦታዎችን፣ ጋርደኖችንና የህፃናት መዋያና የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች… ወዘተ. እየተባሉ ማቀድና መስራት ባልተለመደበትና፣ ሁሉም ነገር በአወቅሁኝ ባይነትና በጉልበት በሚሰራበት አገር አንድ ጊዜ የተጣሉ ወይም የተሰሩ ስራዎችን ለመለወጥና ለማሻሻል በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን የታወቀ ጉዳይ ነው። በተለይም ኮንደሚኒዩም እየተባሉ ካለዕቅድ የተሰሩ የመኖሪያ ህንፃዎችን ለማፍረስና በአዲስ መልክ ለመስራት አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ግብ ግብም እንደሚፈጥር ከአሁኑ መገመት ይቻላል።
ውድ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ ይህችን ትንሽ የቅሬታ ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አሁን በቅርቡ በተባበሩት የአረብ ኢሚራት ገንዘባ አውጭነት በኢግል ሂልስ በሚባለው የህንፃ ተቋራጭ በአዲስ አበባ ከተማ ሊሰራ የታቀደው የመገበያያ ቦታ(Shopping Centre) ስላሳሰበኝ ነው። በመሰረቱ ከአዲስ ህንፃ አሰራርና ከገበያ አዳራሽ ስራ ጋር ምንም ጠብ የለኝም። ጠቤና ችግሬ ግን ይህ ዐይነቱ የመገበያያ ቦታ፣ ወይም በዘመኑ አጠራር ሞል በመባል የሚታወቀው ሊሰራ ሲታቀድ ለመሆኑ አስተዳደርዎ ብቻ ሳይሆን፣ የሚመለከተው የአገሪቱ አገዛዝና የአዲስ አበባ ኗሪ ህዝብ ተወያይቶበታል ወይ? በአስተዳደርዎ ስር ያሉ የሶስዮሎጂ፣ የፍልስፍና፣ የህሊና ሳይንስ፣ የህንፃ አሰራር ኤክስፐርቶችና የከተማ ዕቅድ አጥኚዎችና አውጭዎች… ወዘተ. በበቂው ተወያይተውበታል፣ ወይም ተሳትፈውበታል ወይ? በመሰረቱ እንደዚህ ዐይነት ማዕከልም ሆነ ህንፃ ሲሰራ በአካባቢው ያለውን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ኗሪ ህዝብ የሚመለከት ነው። እርስዎና አስተዳደርዎ የህዝብ አገልጋይ እንደመሆናችሁና፣ ለዚህም ህዝብ ከሚከፍለው ቀረጥ ደሞዝ ስለሚከፈላችሁ የህዝብን ፍላጎት ያላከተተና ከረጅም ጊዜ አንፃር ታስቦ ሳይታቀድ የሚሰራ ስራ ላይ ዝምብላችሁ መደንገግ አትችሉም። የዚህ የገበያ አዳራሽ መሰራት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ 70% የሚሆነውን ወጪ የሚሸፍነው የተባበሩት አረብ ኢሚራት ኩባንያ ነው። ይህም ማለት ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ የኩባንያውንና የጥቂት አረቦችን ፍላጎት የሚያሟላ ነው ማለት ነው። ወደፊትም እነሱ እንደልባቸው የሚዝናኑበትና የጌታና አሽከር መንፈስ የሚፈጠርበት ሁኔታ እንደሚፈጠር መገመቱ ከባድ አይሆንም። እንደሚያውቁትና ህጉም እንደሚለው አንድ የከተማም ሆነ የአገር አስተዳደር ለውጭ ኩባንያም ሆነ ግለሰቦች በመዋዕለ-ነዋይ ስም እያሳበበ መሬት እየከለለ የመስጠት መብት የለውም። ይህ ሊሆን የሚችለው በአገሪቱ ውስጥ ተቀማጭነት ያለውና የአገሪቱን ዜግነት የተቀበለና በልዩ ልዩ ስራዎች በመሰመራት ኃላፊነቱን ያረጋገጠ ከሆነ አንድ የውጭ ሰው በመዋዕለ-ነዋይ ሊሳተፍ የመቻል መብት አለው። አዲስ ይሰራል ወደ ተባለው የመገበያያ ቦታ ስንመጣ ግን ኩባንያው ኢትዮጵያዊ ያለሆነ ነው። ይህም ማለት አስተዳደርዎ ቀስ በቀስ ከተማችንን ወደ ቅኝ-ግዛትነት ይለውጣታል ማለት ነው። ይህ ጉዳይ በዚህ የሚያቆም ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ቀን ደግሞ የሳውዲ ሀብታሞች መጥተው አንድ መንደር እንገንባላችሁ ሊሉ ይችሉ ይሆናል። ከዚህም በላይ ኤንቬስተሮች ነን የሚሉ የውጭ ኩባንያዎች ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ሀብታም የሚሰበስቡትን ገንዘብ አገሮችን በማሰስና ከአገዛዞች ጋር በጥቅም በመጋራት የከተማ ቦታዎችን በመግዛትና ህንፃዎችን በመስራት የየአገሩን ህዝብ የሚያፈናቀሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። እንደዚሁ ዐይነቱ ሁኔታ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚታይና ህዝቦችን ያማረረና ለስደትም ያበቃ ነው። በካፒታሊስት አገሮችም ይህ ሁኔታ አፍጦ አግጦ በመውጣት በከተማዎች ውስጥ ቤት ተከራይቶ መኖር የማይቻልበት ሁነታ ተፈጥሯል። የፋይናንስ ካፒታል የበላይነትን ከተቀዳጀ ወዲህ የየአገሩ መንግስታትና የከተማ ከንቲባዎች ሁኔታውን መቆጣጠር እንዳልቻሉ በቅርብ እየተከታተልን ነው። ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ኃላፊነት የማይሰማቸው የሶስተኛው ዓለም አገዛዞችም ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በማበር ህዝቦቻቸውን መኖሪያና መንቀሳቀሻ እንዳሳጧቸው እየተከታተልን ነው። ስለሆነም ምንም ዐይነት ውይይትና ክርክር፣ እንዲሁም ሰፊ የህብረተሰብ ጥናት ባልተለመደበት እንደኛ ባለ አገር አንድ የውጭ ኃይል ሲመጣና ኢንቬስት ላድርግ ሲል ካለምንም ቅሬታ እሺ ማለቱ የተለመደ ነው። በዚህ መልክ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ለአሜሪካን፣ ለእንግሊዝና ለሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ኤምባሲዎች ጋሻ መሬት እየተሰጣቸው ኤምባሲዎቻቸውን እንዲገነቡ በመደረጋቸው ይህ ጉዳይ በአገራችን ፖለቲካ ህይወትና የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ማሳደር እንደቻለ የታወቀ ጉዳይ ነው። ኤምባሲዎች ሰላዮችም የሚመለመሉባቸው ቦታዎች እንደመሆናቸው መጠን በአገራችን ውስጥ ለተከሰተውና ለሚከሰተው የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዳበረከቱና እንደሚያበረክቱም የታወቀ ጉዳይ ነው። በተለይም በአብዮቱ ወቅት በከተማዎች ውስጥ ብዙ የወጣት ደም ሊፈስ የቻለው በዚህም ምክንያት ነው። በመሆኑም ባለፉት ስድሳ ዐመታት አገራችን የዚህ ዐይነቱ ደካማ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሰለባ በመሆኗ ዛሬ የምናየው አስቀያሚ ሁኔታ ላይ ለመውደቅ እንድትችል ተደርጋለች።
ከዚህ ወጣ ብለን የገበያ አዳራሹን ዕቅድና አሰራር ሁኔታ ስንመለከት ከ1980ዎቹ ዐመታት ጀምሮ በመጀመሪያ ደረጃ በአሜሪካን አገር የተስፋፉ የኒዎ-ሊበራል የገበያ አዳራሾች ዐይነት ሲሆኑ፣ ግሎባላይዜሽን መስፋፋት ከጀመረበት ከ1990ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ ደግሞ በአውሮፓ ከተማዎች በመስፋፋት የባህል ውድመት እንዲከሰት ያደረጉ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በብዙ የአውሮፓ ከተማዎች ቀደም ብለው የነበሩና የሚያማምሩ ህንፃዎችና የባህል ቦታዎች እየፈራረሱ ገንዘብ ላላቸው ኩባንያዎችና የፈንድ አስተዳዳሪዎች ቦታዎች ስለተሰጡ እንደዚህ ዐይነቱ ጊዜያዊ የሆነ፣ ግን ደግሞ ዘላቂነት የሌለው ሞልስ ሊስፋፋ ችሏል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በጣም የታወቁ አርክቴክተሮች ሊበሳጩ ችለዋል። በተለይም ባለፉት 20 ዐመታቱ ሞልስ የሚባሉት የመገበያያ ቦታዎች ከመስፋፋታቸው የተነሳ በሶስይሎጂስቶችና ፈላሳፋዎች እንዲሁም ክሪቲካል አመለካከት ባለቸው አርክቴክቸሮች በሰፊው እየተተቹ ነው። ምክንያቱም የእንደዚህ ዐይነት መገበያያ ቦታ መስፋፋት ሰፊውን ኗሪ ህዝብ ሁሉ ጊዜ የፍጆታ ተጠቃሚ ብቻ ስለሚያደርገውና፣ መጸሀፍ ለማንበብና ከቤተሰቦቹ ጋር ጭንቅላትን ሊያድስ የሚችል ልዩ ልዩ ባህላዊ ነገሮችን እንዳይከታተል ስለሚያግዱት ነው። በመሆኑም በዚህ ዐይነቱ የህንፃ አሰራርና የፍጆታ ዕቃዎች መገበያያ ቦታ መስፋፋት የተነሳ የሰው መንፈስ እየረጋ የመጣ ሳይሆን አመፀኛ እየሆነ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። በታሪክ ውስጥ እንደታየው ይህ ዐይነቱ የገበያ አዳራሽ ያልተስፋፋባቸው ከተማዎችና ቦታዎች እንዲሁም በማዕከለኛው ከፍለ-ዘመን ታስበው የተሰሩ ህንፃዎች ባሉበት ቦታዎች የሰው መንፈስ የረጋ እንደሆነ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በእንደነዚህ ዐይነት የከተማ አገነባቦች ፈላስፋዎች፣ ሶስይሎጂስቶች፣ የህግ አዋቂዎች፣ የከተማ ዕቅድና አርክቴክተሮች የተሳተፉባቸውና ተግባራዊ ያደረጓቸው በመሆናቸው ሁሉንም ነገር ያካተቱ ናቸው። ዘለዓለማዊነት ያላቸውና የማይሰለቹም ናቸው። አሁን በአንድ ባይሎጂስት ተጠንቶ በቀረበ ሰፊ ጥናት መሰረት፣ በተለይም ሁሉንም ነገር ያላካተቱ ከተማዎች ማለትም፣ ጋርደኖችና ዛፎች ያልተስፋፉባቸው፣ ድልድዮችና ወንዞች የሌሉባቸው፣ ሰፊው የከተማ ህዝብ እንደልቡ በእግሩና በቢስኪሌት ሊንቀሳቀስ የማይችሉባቸው የህንፃ አሰራሮችና፣ ፈታ ፈታ ብለውና የተወሰነ የጂኦሜትሪ ህግን በመከተል ባልተሰሩባቸው ከተማዎች የሰው መንፈስ እንደሚረበሽ ነው። ባይሎጂስቱ በኦቲዝም የተያዘ ልጅ ስላለው ይህንን በሚገባ ለማረጋገጥ ችሏል። ማለትም ልጁ ዛፎችና ወንዞችን ሲያይ ወይም ወደ ጫካ በሚሄድበት ጊዜ መንፈሱ ረጋ ሲል፣ ወደ ከተማ ሲመጣ ደግሞ እንደሚረበሽ ነው። በኤክስፐርቱ ዕምነትና ጥናትም መሰረት በከተማዎች ውስጥ የግዴታ መናፈሻ ቦታዎች፣ የመርከብ መንቅሳቀሻ ወንዞችና ድልድዮች፣ ለሰው መንቀሳቀስ አመቺ ሆነው የሚታቀዱና የሚገነቡ ከተማዎች ያለፈባቸው ጥያቄዎች ሳይሆኑ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄዎች እንደሆኑ ነው። ከዚህ ስንነሳ የሞል መስፋፋት ጊዜያዊ የሆነና ለማህበራዊ ግኑኝነትና ለባህል ዕድገት የሚያመች አይደለም። የሚሰለችና መንፈስን የሚረብሽና ለአመጽ መስፋፋትም የሚያመች ነው።
በከተማችን እንደዚህ ዐይነቱ ዘመናዊ የሚመስል በመሰረቱ ግን ፀረ-ባህል የሆነ የህንፃ አሰራር ሲሰራና አንድ ቀን ተመርቆ ሲከፈት ሱቆቹ በሙሉ አገር ቤት ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች የሚሞሉ ሳይሆኑ፣ ከውጭ አገር በሚመጡ ዕቃዎች ነው። ይህም ማለት አገሪቱ ከፍተኛ የንግድ ሚዛን መዛባት የሚደርስባት ብቻ ሳይሆን ከፍጆታ አጠቃቀም ባህል አንፃርም በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ክፍተትን ሊያመጣ ይችላል። በሱቆች ውስጥ የሚደረደሩትንና የሚያብረቀርቁ ዕቃዎችን ገዝቶ ሊጠቀም የሚችለው ገንዘብ ያለው ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ ደግሞ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ የሚያድስ ሳይሆን እንዲያውም በፍጆታ አጠቃቀሙና በገንዘብ አወጣጡ የሚዘባነን የህብረተሰብ ክፍል በመፈጠር ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል የህብረተሰብ ግጭት ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው። ሰሞኑን ደግሞ እንደዚሁ አሜሪካና አውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድ አክሲዮን በማቋቋም እንደዚሁ የመገበያያያ ማዕከል ለማቋቋም እንዳቀዱ ዜናው ተስፋፍቷል። በመገበያያው ቦታ ውስጥም ስምንት መቶ ሱቆች እንደሚከፈቱ ዕቅድ አለ። ያኛውም ሆነ ይኸኛው የገበያ አዳራሽ በመሰረቱ ከምርት ክንዋኔ ጋር የተያያዙ ሳይሆኑ የፍጆታ ዕቃ ማራገፊያዎች ብቻ ናቸው ማለት ነው። የአገር ውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ የሚያስችል አቅም አይኖራቸውም። በአንድ አገር ውስጥ ገበያ በተለያየ መልክ ሊያድግና ህብረተሰቡን ልያስተሳሰር የሚችለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ ሲካሄድ ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአጠቃላይ ሲታይ የስራ መስክ መክፈቱ ብቻ ሳይሆን በገቢ ማደግና በፍጆታ ግዢ በተያያዘ ሁኔታ የአገር ውስጥ ገበያ በዐይነትም ሆነ በመጠን ያድጋል፤ ይስፋፋልም። ከዚህም ባሻገር ከአገልግሎት መስክ ይልቅ የምርት ክንዋኔ መስፋፋት የፈጠራ ስራን ማዳበሩና ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም መፈጠር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ በራሱ ደግሞ የአገልግሎት መስኩ እንዲስፋፋና ከምርት ክንውን ጋር እንዲያያዝ በማድረግ የገንዘብን በፍጥነት መሽከርከርና መጠንከር ያስከትላል ማለት ነው።
ወደ ሌሎች ጉዳዮች ስንመጣ የገበያ አዳራሾች ሲስፋፉ ያለውን የውሃ መጠንና መብራት ስለሚጋሩ እስካሁን ድረስ እንደተከታተልነው ለተጠቃሚው ህዝብ አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን የመፍታት ችግር ያጋጥማል። ይህ ጉዳይ በተለይም በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገር ከተማዎች የሚታይና አብዛኛው የከተማ ኗሪ ህዝብ ቆሻሻ ውሃ እንዲጠጣ የተገደደበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ባለፉት 27 ዐመታት በአዲስ አበባ ከተማችንም የሚታየው ጉዳይ ይህ ነው። ካለምንም ዕቅድ በመስታወት የተጠቀጠቁ ህንፃዎችና ሆቴል ቤቶች በመሰራታቸው በከፍተኛ ደረጃ ውሃንና ኃይልን ሊጋሩ ችለዋል። በተለይም የቴክኖሎጂ ምጥቀት በማይታይበት አገርና፣ አንዳንድ ችግሮች ሲከሰቱ ለመቅረፍ በማይቻልበት አገር እንደዚህ ዐይነት ህንፃዎችን መስራት የዘመናዊነት አስተሳሰብ ሳይሆን ኋላ-ቀርነትን ነው የሚያመለክተው። እዚህ ላይ የሚገርመው ግን ኢትዮጵያውያን ኢንቬስተሮች ለምን ወደ ሌላ የክልል ከተማ ሄደው እንደማይሰሩ ነው። አዲስ አበባ እንደሆን በሆቴል ብዛት ጥቅጥቅ ከማለቷ የተነሳ ወደፊት ሆቴል ቤቶች ትርፋማ የማይሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ኢትዮጵያውያኖች ለአገራችን ዕድገት የሚያስቡ ከሆነ በቴክኖሎጂና በማሽን ኢንዱስትሪ ላይ ገንዘባቸውን ቢያፈሱ ከረጅም ጌዜ አንፃር አገራቸውንም ሆነ እራሳቸውን ሊጠቅሙ ይችላሉ።
ከዚህና ከሌሎች የአገር ዕድገት ጉዳይ ስንነሳ እንደዚህ ዐይነቱ የመገበያያ ቦታ መሰራቱ ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝባችንም ፍላጎት አይደለም። ህዝባችንም ይህንን ተመኝቶና ይሰራልኝ ብሎ ድምጹን ከፍ ብሎ አላሰማም። የህዝባችን ፍላጎት በመጀመሪያ ደረጃ በደንብ የታቀደና ዘላቂነት የሚኖረው መጠለያ ቤት ማግኘት ነው። ጥንታዊውና ትክክለኛውም መንገድ ይህ ነው። የሰውን መሰረታዊ ችግር ሳይፈቱና ዘላቂነት ያለው ከተማ ሳይገነቡ ዕውነተኛና የተስተካከለ ዕድገት ማምጣት በፍጹም አይቻልም።
ስለሆነም የአዲስ አበባን ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማንና አስተዳደራቸውን የማሳስበውና የምጠይቀው የከተማውን ኗሪ የሚመለከት ነገር ከማቀዳችሁና ተግባራዊ ከማድረጋችሁ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ከሁሉም አንፃር ማሰብ መቻል አለባችሁ። ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የከተማ ዕቅድ አውጭዎችና አርክቴክተሮች፣ ግን ደግሞ የክላሲካል ህንፃ አሰራርና የሰብአዊነት አስተሳሰብ ካላቸው ጋር በመወያየት ከተማዎችን መገንባት ይቻላል። ከትርፍ አንፃር የሚገነቡና ህዝብን የሚጋፉ የግንባታ ስራዎች ህብረተሰብአዊ ውዝግብን የሚፈጥሩ ብቻ ስይሆኑ የሚረብሹም ናቸው። ከዚህና ከሌሎች አያሌ ጉዳዮች ስነሳ በተለይም በተባበሩት የአረብ ኢሚራትስ ኩባንያ የሚሰራው የገበያ መንደር በአስቸኳይ መቆም ያለበት ጉዳይ ነው። ከባህላችን ጋር የማይሄድ ብቻ ሳይሆን፣ ብሄራዊ ነፃነታችንንም የሚገፈን ነው። በባህል እንዳናድግና ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን በመስራት የተስተካከለ ዕድገት ባለቤት እንዳንሆን የሚያግደን ነው።
ከማክበር ሰላምታ ጋር
ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለሙያና የስልጣኔ ተመራማሪ
fekadubekele@gmx.de