[gtranslate]

ፖለቲከኛ ነን ባዮች በፖለቲካ ስም የሚሰሩት ትልቅ የታሪክ ወንጀል-ክፍል ሶስት!!

ሃይማኖት፣ ፖለቲካና ህብረተሰብ

                                             ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                       መስከረም 11  2020

መግቢያ

      የዐለማችን ሁኔታ በጣም እየተወሳሰበ መጥቷል። በየአገሮች ውስጥ የማህበራዊና የፖለቲካ ጥያቄዎች ሳይፈቱ የሃይማኖት ጥያቄ ራሱን የቻለ አጀንዳ ሆኖ በመምጣት ብዙ አገሮችን እያተራመሰ ነው። በተለይም የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ ያለው የፖለቲካ አወቃቀር ምሁራዊ ብስለት ስለሚጎድለው፣ አፍጠው አግጠው የሚመጡ እንደ ሃይማኖት የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በውውይትና በክርክር ከመፍታት ይልቅ ግብግቡ ወደ አመጽ በማምራት አክራሪዎች በሚባሉትና በመንግስታት መሀከል የሚደረግ ዐይነት ፍጥጫ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። መንግስታት ወደ ዕምነት ያመራውን የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል በጭፍኑ በአክራሪነት በመወንጀል በተለኮሰው እሳት ላይ ቤንዚን እየነሰነሱበት ነው።

      በተለይም ግሎባል ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ ከዛሬ ሃያ ዐመት ጀምሮ ዓለምን በአንድ አመለካከት ለማዋቀር የተወሰደው ርምጃ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣና፣ ብዙ ህብረተሰቦችን እያተራመሰ እንደሚገኝ ለሁላችንም ግልጽ ነው። „ሊበራል ካፒታሊዝም“ ወይም ኒዎ-ሊበራሊዝም በአሽናፊነት ከወጣ ወዲህ በየአገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ከውስጥ ህብረተሰብአዊ መረጋጋትን የሚያስከትሉ አልሆኑም።ኢኮኖሚ ፖሊሲው በፈጠረው ያለተስተካከለ የዕድገትና የሀብት ክፍፍል የተነሳ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩና ጥቂት ተጠቃሚዎች በፈጠሩት አንድነት በብዙ ሚሊዮን የሚጠጉ ህዝቦችን ወደ ድህነት ዓለም እየገፈተሩና፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በተለያየ አልባሌ መስክ ሲሰማሩ፣ የተወሰነው ደግሞ ሃይማኖትን ጥገኛ በማድረግ የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ዕምነት ተከታይ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። ለአንዳንዶች ሃይማኖት እንደ ዕምነት ከመታየት ይልቅ እንደ ችግር ፈቺነት እየታየ እንደመጣም መገንዘብ ይቻላል።

      በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለው ምሁራዊ ክፍተትና የነገሮችን በጥልቀትና በሰፊው አለማሰብ መቻል፣ እንዲሁም ደግሞ ድንቁርና በሚመስል መልክ የሚካሄድ ፖለቲካ እንደ ናይጄሪያ፣ ማሊና ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የመሳሰሉትን የበለጠ ወደ ሃይማኖት መዋከቢያ መድርክ እየቀየራቸው ነው። በነዚህ በተለያዩ አገሮች ያለው የፖለቲካ አወቃቀር የተለያየ ቢመስልም፣ በሁሉም አገሮች ያለው በሃይማኖት ተሳቦ የሚካሄደው እንቅስቃሴና ውዝግብ በመሰረቱ ከፖለቲካ አወቃቀር(Political Engineering)፣ ከኢኮኖሚ  ፖሊሲ ስህተትና፣ ይህ የሚፈጥረው የተዛባ የማህበራዊ ኑሮና፣ በጥቂት ሰዎች ዘንድ የሀብት ክምችት የሚወልደው ብሶት ነው ማለት ይቻላል።  በተለይም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት መውጣት በአክራሪነት ስም አሳቦ ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል። ዘመኑ በርዕዮተ-ዓለም መሀከል የሚደረግ ሳይሆን በምዕራቡ የሊበራል ካፒታሊዝምና በእስላሙ ዓለም ስለሆነ (The Clush of Cultures) ፍጥጫው በአዲስ መልክ መካሄድ እንዳለበት ከተወሰነ ዐመታት አልፎታል። በተለይም ደግሞ እንደ ቻይና የመሳሰሉት እንደ ኃያል መንግስትነት ሆኖ መውጣትና ጥሬ ሀብቶችን ወደ መቆጣጠር ማምራት በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የምዕራቡ ዓለም ስትራቴጂውን በአዲስ መልክ እንዲቀይር አስገድዶታል።  ስለሆነም በሃይማኖትና በአክራሪነት አሳቦ አፍሪካን ወደ ጦር አውድማነት ወደመለወጥ እያመራ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም አፍሪካን በአዲስ መልክ ማመሱ ወሳኝ ሚናን አየተጫወተ በመምጣት ላይ ነው። በተለይም ከስምንት ዐመታት ጀምሮ የተከሰተው የፊናንስ ቀውስና፣ በአሁን ወቅት ደግሞ የኦይሮ አገሮችን የሚያመሰው የዕዳ ትብትብና፣ ይህንን በአገሮች ጥረት ሳይሆን የበለጠ የአንጀት አጥብቅ ፖለቲካ በመከተል ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው የዓለም አቀፍ አስተዳደር(World Governance)  የፈጠረው ሁኔታ፣ በየቦታው ከሚታየው የሃይማኖት ውዝግብ ጋር ተደምሮ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ እየተባለ የሚጠራው ዓለምን ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታ ፈጥሮለታል። በዚህ መልክ የአፍሪካ ህዝቦች የሰላም፣ የስልጣኔና የዕድገት፣ እንዲሁም ህብረተሰቦቻቸውን በአዲስ መልከ የመገንባቱ ጉዳይ ለብዙ መቶ ዐመታት መተላለፍ አለበት የሚል ውሳኔ ላይ የተደረሰ ይመስላል።  የምዕራቡ ዓለም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአሸናፊነት ወጣሁ ብሎ ያለተመጻደቀውን ያህል የአፍጋኒስታኑ ጦርነት ከከሸፈ ወዲህ፣ እንደገና ደግሞ ብዙ የአፍሪካ አገሮች እንደ ህብረተሰብና እንደ ኢኮኖሚያዊ ቅንጅት ሆነው እንዳይዳብሩና እንዳይበለጽጉ ወደ ጦርነት እንዲለወጡ ሁሉ ነገር ተዘጋጅተውላቸዋል። የብዙ አፍሪካ አገሮች ዕድል አዲስ በወጣችውና የጥሬ-ሀብትን ለመቃረም ከተለያዩ የአፍሪካ መንግስታት ጋር ስምምነት  በተፈራረመችውና፣ እያረጀ በሄደው ኃያል መንግስት መሀከል በሚደረግ ፍጥጫ የሚወሰን ይሆናል። ይሁንና ግን የአክራሪዎችን መስፋፋት ተንተርሶ አሜሪካ ለቻይና አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር ብዙ አገሮችን በጦርነት ወጥመድ ውስጥ እየከተተ ይገኛል።

      ይህንን ያልተረዱ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች በራቸውን ክፍት በማድረግ በቀላሉ ሊወጡ ወደማይችሉት ወደ ሃማኖት ግብግብነት እያመሩ ነው።  እንደ ኒጀርና ኢትዮጵያ የመሳሰሉት አገሮች ካለምንም ህጋዊ ፈቃድ አሜሪካ እንዲተክል የፈቀዱለት የሰው-አልባ የጦር አውሮፕላኖች ካምፕ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ለማመስ የሚያመችና የቻይናን ሽቅድምድሞሽ ለመዋጋትም ጭምር የሚያገለግል ነው። ይሁንና ግን ደግሞ ይህ ዐይነቱ በመንግስታት ሳይታሰብ የተሰጠ የጦር ካምፕ እንደ ኢትይጵያ የመሳሰሉትን አገሮች የፓኪስታን ዐይነት ሁኔታ የሚፈጠርባቸው ይሆናሉ። ምናልባት ከረዥም ጊዜ አንፃር እንደ አልቃይዳና አይሲስ የመሳሰሉት የውስጥ ለውስጥ በስለላ ድርጅቶች የሚደገፉ የሚፈለፈሉበትና አገር የሚያምሱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በመሰረቱ ግን ጥያቄው የሃይማኖት ሳይሆን የፖለቲካ፣ የተበላሸ ሀብትን የሚያወድም የኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ ይህ ያስከተለው የማህበራዊ ጥያቄ ለመሆኑ ለብዙዎቹ ግልጽ የሆነ አይመስልም። ስለዚህም ይህንን አስቸጋሪና የተወሳሰበ ጥያቄ ለመረዳትና መልክ ለማሲያዝ በጥሞና መወያየት የሚያሰፈልግ ይመስለኛል። ውይይቱ ከፍተኛ ምሁራዊ ብስለትና ውስብስብነቱን በመረዳት በሰፊውና በግልጽ መወያየት መደረግ ያለበት ይመስለኛል። በአጭሩ የፖለቲካ ጥያቄ እስካልተመለሰና፣ እየተወሳሰበ የመጣውንና፣ በምዕራቡ ዓለምና በናጠጡ የአረብ መንግስታትት የሚሸረበውን ተንኮል እስካለተረዳንና ለመወያየት ዝግጁ እስካልሆን ድረስ አገራችን ወደ ትርምስ ዓለም እንደምታመራ ካሁኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ ስለ ሃይማኖትም ሆነ ስለፖለቲካ ያለኝን ግንዛቤ አጠር ባለ መልክ ላቅርብ።

የሃይማኖት ሚናና ጥያቄ !

      እንደሚታወቀው የሃይማኖት ዕድሜ ከፍልስፍና ጋር ሲወዳደር አጭር ነው።  ከስድስት መቶ ዐመታት ከክርስቶስ ልደት በፊት የፍልስፍና ጥያቄ ሲነሳ፣ ከዚያ በፊትም ሆነ በጊዜው የነበረውን ችግር፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ በሀብት መባለግ፣ ድህነትና ኋላ- ቀርነት መረዳት የተቻለው የሰው ልጅ አስተሳሰብ በማይረባ ነገር ስለተወጠረና፣ አርቆ የማሰብ ኃይሉም ደካማ ስለሆነ ጦርነትንና ስግብግብነትን በማሰቀደም ታሪክን ለመስራት እንዳማይችል በመሆኑ ነበር የታመነው። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው የነበረው አገዛዝም ሆነ ህዝብ፣ ከየት እንደ መጡ፣ ለምን በዚህች ዓለም ላይ እንደሚኖሩና፣ ወዴትስ እንደሚያመሩ ራሳቸውን ለመጠየቅ የሚችሉ ኃይሎች አልነበሩም። ስለሆነም ጦርነት እንደተፈጥሮ ህግና እንደባህል በመወሰድ፣ እርስ በርስ በመተራረድ በመፈንደቅ የሚሽለልበትና፣ ገዳዩም እንደጀግና የሚቆጠርበት ዘመን ነበር። ፈላስፎች ብቅ ሲሉና ይህንን ዐይነት ችግር ሲመረምሩ የሰው ልጅ ችግር የማሰብ ኃይል ችግር መሆኑን በመረዳት፣ ተፈጥሮንንም ሆነ የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል፣ እንዲሁም ደግሞ የህብረተሰብን አወቃቀር ለመረዳት ከፍተኛ ምርምር ያደርጋሉ። በፈላስፋዎች አመለካከት ከተፈጥሮ በስተቀር ህብረተሰብአዊ አወቃቀሮች የሰው ልጅ ውጤቶች ናቸው። ከዚህም በላይ ፖለቲካም ሆነ ሌሎች እንደባህል የመሳሰሉ ነገሮች በተፈጥሮ ውስጥ ከተፈጥሮ ጋር የተወለዱ ሳይሆኑ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሰፈነው አስተዳደርና የየህዝቦች አኗኗር የሚፍጥረው ውጤት ነው። እንደንቃተ ህሊናቸው ማደግና አለማደግ፣ ህብረተሰቦች አይ ጥበባዊና እኩልነት የሰፈነባቸው ሆነው ይዋቀራሉ፣ ካሊያም ደግሞ የተበላሹና የተዝረከረኩ፣ እንዲሁም ዓላማ ቢስ ሆነው እየተዋከቡ ይኖራሉ። በተለይም ከአምስት መቶ ዐመት ከክርስቶስ መወለድ በፊት የነበረው የግሪኩ ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። በተጨማሪም የሮማውያን አገዛዝ ለመጨረሻ ጊዜ በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በራሱ ውስጥ ባለው መባለግና በጊዜው ባልስለጠኑት የጀመርን ህዝቦች ወረራ ሲደርስብት ሲፈረካክስና ሲበታተን አዲስ ሁኔታ ተፈጥሮ የአውሮፓን ህዝብ ለብዙ መቶ ዐመታት በጨለማው ዘመን ውስጥ እንዲኖር ይደርገዋል። ለሰባት መቶ ዐመታት ያህል የካቶሊክ ሃይማኖት የፈጠረው ጭፍን አገዛዝና ዕምነት የአውሮፓን ህዝቦች ሲያምስና፣ ለረሃብና ለድንቁርና በመዳረግ የስልጣኔውን ዘመን ያራዝማል። የጥቁር ሞት(Black Death) የተሰኘው የተስቦ በሽታ በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ሶስተኛውን ያህል ህዝብ ይጨርሳል። ይህ ሁሉ ዕልቂት ሊደርስ የቻለው በዕውቀት ማጣትና በገዥዎች መባለግ እንደሆነ ዳንቴና የሱን ፈለግ የተከተሉ ይደርሱበታል።

        በአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓው ውስጥ በጊዜው የነበሩና ብቅ ያሉ ፈላስፎቸ አዲስ የተከሰተውን ሁኔታና የኃይል አሰላለፍ እንዲሁም የአገዛዞችን ባህርይ፣ ልክ እንደ ግሪክ ፈላስፎች መመርመር ይጀምራሉ። የተፈጥሮን ህግ ለመረዳት የበለጠ ጥናት ያደርጋሉ። የደረሱበትም ውጤት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን ስለማይጠቀምና የተፈጥሮን ህግጋት ስለማይረዳ እንደዚህ ዐይነቱን ጭፍን ዕምነትና የኑሮ መመሰቃቀል እንደሚፈጥር ይደርሱበታል። ከዚህ ዐይነቱ ውዥንብር መውጣት የሚቻለው የሰው ልጅ ብርሃኑን ለማየትና ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን ለመስራት እንዲችል የግዴታ በአዲስ ዕውቀት መታነፅ እንዳለበት ያመለክታሉ፤ ያስተምራሉም። በጊዜው የነበረውን ጭፍን ዕምነትና አመለካከት በዲያሌክቲካዊ ምርምርና በሳይንስ መጋፈጥ ይጀምራሉ። ዕውነትን ከውሸት ነጥለው በማውጣት የስልጣኔውን ፋና ለማሳየት በቆራጥነት ይነሳሉ። በዚህም በተለይም በሃይማኖትና በፖለቲካ አካባቢ ያሉ መሪዎችን ለማሳመን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ይረዳሉ። ይሁንና ከአመጽ ይልቅ ፍቱኑ መንገድ እየሰሩ ማስተማር የሚለውን መንገድ በመከተል አንዳንድ በአገዛዝና በሃይማኖት አካባቢ ያሉ ሰዎችንም ማሽነፍ ይችላሉ። በማይቻልበት ቦታ ደግሞ ብዙ ምሁራን ወደ እስርቤት በመወርወርና በመቃጠል የተመኙትን ሳያዩ ህይወታቸውን ያጣሉ።

       በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ለአውሮፓ የስልጣኔ ታሪክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት በከፍተኛ ዕውቀት ይመሩ የነበሩት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንደነበሩ ታሪክ ያረጋግጣል። የግሪክን ፍልስፍናን ሳይንስን ከግሪክኛ ወደ አረብኛና ወደ ላቲን በመተርጎም ለአንዳንድ የአውሮፓው የካቶሊክ ምሁራን ተከታዮች በማቅረብ ሰፊ የመመራመሪያ መድረክ ይከፍታሉ። በዚህም መሰረት በተቻለ መጠን ሃይማኖትንና ፍልስፍናን ለማስታረቅ ወይም ለማዛመድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የሳይንስ ምርምር ቀስ በቀስ ይስፋፋል። በምርምሩ አማካይነት ከዚህ ቀደም የነበሩ ጭፍን ዕምነቶች በሙሉ ቀሰ በቀስ ተቀባይነት በማጣት የካቶሊክ ሃይማኖት ዕምነት እንዲገፋና የበላይነቱን እንዲያጣ ይደረጋል። የእስላም መምህራን በሚገዙበት እንደ ደቡብ ስፔይን በመሳሰሉት ቦታዎች ከምንም በመነሳት አዲስና ልዩ ስልጣኔ ይገነባሉ። ታላላቅ የእስላም የሃይማኖት መሪዎች የእስልምናን ሃይማኖት በጭፍኑ የሚሰብኩ ሳይሆኑ፣ የተለያዩ ዕምነት ያላቸው ህዝቦች ተስማምተው እንዲኖሩ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ መገንባት ይጀምራሉ። የምርምር መጽሀፎችን በማስፋፋት በዕርግጥም ድንቅ ድንቅ ስራዎችን ይሰራሉ። በደቡብ ስፔይን ያለው አላሃምብራ የሚባለው ግሩም ቦታና ግንቦች፣ በኮርዶባና ካዲስ፣ እንዲሁም ሲቪሊያ የሚታዩት ጋርደኖችና ቤተመንግስታት፣ እንዲሁም ካቴድራል የእስላም የሃይማኖት መሪዎች የስልጣኔ ውጤቶች ናቸው። ይሁንና ግን ይህ ለአውሮፓው ስልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው የእስልምና ሃማኖት በካቶሊክ የሃይማኖት መሪዎች ጦርነት ተከፍቶበት መጨረሻ ላይ መበታተን ይጀምራል። የእስልምና ሃይማኖት እስከ አስራ አምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በሳይንስ፣ በአስትሮኖሚ፣ በማቲማቲክስና በህክምና የነበረውን የተቀዳሚነት ቦታ ያጣል። አንድ ቦታ ላይ መርጋት ያልቻለው አመራር በመበታተን፣ የሳይንስን ትርጉም የሚጠይቁና የሃይማኖትን የበላይነት የሚያስቀድሙ አዳዲስ ኃይሎች ቀስ በቀስ አይለው በመውጣት የእስላም ሃይማኖት በስልጣኔ ረገድ የነበረውን ግንባር-ቀደምትነት እንዲያጣ ይደረጋል።

        ወደ አፍሪካ ስንመጣ፣ ኢትዮጵያችንንም ጨምሮ በዚያ የተስፋፋው የእስልምና ሃይማኖት እንደ አውሮፓው የእስልምና እንቅስቃሴ የስልጣኔ ሚና የነበረው አልነበረም። ከግሪኩ ስልጣኔ ጋር ያልተዋወቀ ስለነበር ወደ ንግድ፣ በተለይም ወደ ባሪያ ንግድ በማምራት ከአውሮፓው የባሪያ ንግድ ጋር ተደምሮ የአፍሪካን ስልጣኔና የህብረተሰብ አወቃቀር ያዘበራርቃል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር አፍሪካዊ ተሟጦና እስከዚያ ድረስ የገነባውን የስራ ክፍፍልና የንግድ ልውውጥ ድምጥማጡን በማጥፋት ዕድገቱ እንዲቋረጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። በሌላ አነጋገር፣ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችና ወደ ኢትዮጵያ የተስፋፋው የእስልምና ሃይማኖት ስልጣኔው አይ ውስን፣ ካሊያ ደግሞ በዕውቀት ያለተደገፈ ስለነበር ዕድገትን አፋኝ ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህ የሆነው ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከዕውነተኛ ዕውቀት ጋር ባለመጋጨቱ ብቻ እንጂ የሃይማኖቱ ውስጣዊ ባህርይ እንዳልሆነ አንባብያን እንዲገነዘቡልኝ አሳስባለሁ። ልክ እንደካቶሊኩ ሃይማኖት ወደ ተቀሩት የአፍሪካ አገሮችና ወደ ኢትዮጵያ የተስፋፋው ለስልጣኔ የነበረው አስተዋጽኦ ውስን ነበር ማለት ይቻላል።

         የእስልምና ሃይማኖት ከክርስትና ሃይማኖት በኋላ የመጣና ቀስ በቀስ የተስፋፋ በመሆኑ ህብረተሰብአዊ ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለው ዘግይቶ ነው ። ይሁንና ግን በኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የክርስትና ሃይማኖት ለብዙ መቶ ዐመታት የተቀዳሚነትን ቦታ ቢይዝም፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ እስከዚህም ከፍተኛ ግፊት ስላልተደረገበት ከውስጥ ተሃድሶ ሊያደርግና የኢትዮጵያን ዕድገት ሊያፋጥን አልቻለም። በአንዳንድ አካባቢዎች የተደረጉት ሙከራዎች ለውጥን በማይፈልጉ ቀሳውስት ሊዳፈን ችሏል። እንደነ ዘርአቆብ የመሳሰሉት በጊዜው የተገለጸላቸው ፈላስፎችና የሃይማኖት መሪዎች በተደረገባቸው ክትትል ዋሻ ውስጥ ተሸሽገው እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ስለሆነም የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች በድሮው መልኩ በመመራትና ጭፍን አስተሳሰብን በማስተማር ለምርት ሃይሎች አለማደግ፣ ለከተማዎች አለመገንባት፣ ለዕደ-ጥበብ አለመዳበር፣ በህዝቡ ዘንድ በምርትና በንግድ አማካይነት ትስስር እንዳይኖር ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ሚና ይጫወታሉ። የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች ከነገስታቱ ጋር በመቆላለፍና፣ በአንዳንድ ወቅትም የጥገኛ ለውጥ እንዳይካሄድ ከባላባቱ ጋር በማበር ያደርጉ የነበረው እጅግ አስቸጋሪ ሂደትና የቤተክርስቲያን አወቃቀርና ዕምነት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ስነ-ስርዓት  ባለው መልክና ጥበባዊ ሆኖ እንዳይዋቀርና እንደ ህብረተሰብና እንደ ህብረ-ብሄር እንዳይገነባ ገድግደው ይዘውት እንደነበር ይታወቃል። እስከዛሬም ድረስ በአገራችን ምድር ያለው ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ የኋሊት ጉዞ በመሰረቱ ከዕውነተኛ ዕምነት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ በህብረተሰባችን ውስጥ ያለው ሁኔታ ያስረዳል። በመሰረቱ ማንኛውም ሃይማኖት ይሁን ሰብአዊነትንና እኩልነትን የሚያሰተምር መሆን አለበት። ከተንኮል የጸዳ መሆን አለበት። የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሄር አምሳል ነው የተፈጠረው የሚለውን በመስበክና በማስተማር ጭቆናን ለማስወገድ መጣር አለበት ። በማህበራዊ መስክ በመሰማራት የተበደለውናና የተጎዳውን በመርዳት መጠለያ የሚሰጥ መሆን አለበት። የዕውቀትን ብርሃን የሚከፍት መሆን አአለበት። ይሁንና ግን የሚታየው ተንኮለኝነትና መጠፋፋት፣ እንዲሁም ስግብግብነት በአገራችንም ሆነ በውጭ በአንዳንድ አማኝ ነን በሚሉት ዘንድ በመስፋፋት ለመተባበርና ከሃይማኖት ባሻገር ለስልጣኔ የሚደረገውን ሂደት እስከተወሰነ ድረስ በማጨናገፍ ላይ ይገኛል።  በሌላ ወገን ግን የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ዕድገት ህዝባዊ መተሳሰርም ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ መታወቅ ያለበት ጉዳይ መሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። በማንኛውም ረገድ ሃይማኖትም ሆነ ሌሎች ለአንድ ህብረተሰብ የሚያስፈልጉ ነገሮች፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ፖሊሲ መሻሻል ወይም ተሃድሶ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሃይማኖትም በየጊዜው መሻሻልን ካላገኘ ከጊዜ ብዛት በኋላ ተቀባይነትን እያጣ ሊሄድ ወይም ደግሞ በሌሎች ሃይማኖትች የመቀደምና ትርጉም የማጣት ዕድል ሊያጋጥመው ይችላል። ዛሬ በአገራችን ያለው በሃይማኖቶች መሀከል ያለው ፉክክርና የህዝቡ ግራ መጋባት ይህንን ሁኔታ ነው የሚያረጋግጠው።

የእስልምናም ሃይማኖትም ውስጣዊ(Internalized) በመሆንና ተቀባይነት በማግኘት ከዕምነት ባሻገር ለኢትዮጵያ የስልጣኔ ዕምርታ ይህንንም ያህል ያስመዘገበው ነገር የለም። ሁለቱም ሃይማኖቶች የህብረተሰብአችን ውጤቶች በመሆናቸውና፣ ይበልጥ በፊዩዳላዊ የዘልማድ አኗኗር ስልት የታቀፉ ስለሆነ አረማመዳችንን ወስናውል፤ በሰፊውና በጥልቀት እንዳናስብ እንቅፋት ሆነውብናል፤ ፈላስፋዎች፣ ደራሲዎችና የሳይንስ ሰዎች እንዳይፈጠሩ አድርገዋል ማለት ይቻላል። ይህ ተራ ውንጀላ ሳይሆን በህብረተሰብ፣ በባህልና በታሪክ ጥናት(Socio-Cultural Studies)፣ እንዲሁም ደግሞ በንጽጽር ጥናት(Comparative Studies) መነፅር ሊገመገምና ሊረጋገጥ የሚችል ነው። በዚህም መልክ ብቻ ነው መታረምና አንድ በፀና መሰረት ላይ ሊቆም የሚችል ህብረተሰብ መገንባት የሚቻለው። አንገትን ደፍቶ መቀበልና እንዳላዩ ማለፍ፣ ወይም ጥፋት ሲደርስ ዝም ማለት የአዋቂነት ወይም የአርቆ አሳቢነት መለኪያ ሳይሆን፣ በተቃራኒው አንድ ህብረተሰብ እንዲወድም የበኩልን አስተዋፅኦ እንደማበርከት ይቆጠራል።

        እንደገና ወደዚሁ የክርስትና ሃይማኖት ጋ ስንመጣ አብዮቱ እስከፈነዳ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ በመንግስትና በክርስቲያኑ ሃይማኖት መሀከል መቆላለፍ እንደነበር ይታወቃል። ይህ መቆላለፍና መደጋገፍ ከትውልድ ወደትውልድ የተላለፈ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዐመታት በላይ ዘልቆ የቆየ ሁኔታ ስለነበር፣ ችግሩን መረዳት የሚቻለው እንዲያው በጭፍኑ ብሄረሰቦች ተጨቁነዋል ይባል እንደነበረው ሁሉ፣ በመበደልና በመበደል፣ ወይም በመጨቆንና በመጨቆን የሚታይ ሳይሆን፣ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከአስቸጋሪው የህብረተስብአችን አወቃቀር ጋር ማያያዝ የቻልንና፣ የተሃድሶንና(Renaissance) የሪፎርሜሽንን ጉዳይ የአካተትን እንደሆን ብቻ ነው። ካለብዙ ጥናት በደፈናው የእስላሞችን መጨቆን ለማሳየት የሚደረገው ሙኩራ ለችግራችን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ይህ ማለት ግን በህብረተሰብአችን ውስጥ ዝም ብሎ የተወሰደና ተቀባይነት ያገኘ የእስልምናን ሃይማኖት ዝቅ አድርጎ የመመልከት ባህል እንደነበር መካድ አይቻልም። በሌላ ወገን ግን በሁለቱም ሃይማኖቶች መሀከል መከባበርም፣ በክርስቲያኑና በእስላሙ ዘንደ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከመጋባትም ድረስ ጥሩ ባህል እንዳለ ይታወቃል። እንደ ዕውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ እስላሞች በተፈጥሮ ሊበራሎች እንደሆኑ እኛ ከእስላም እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ጋር አብረን ያደግን በደንብ እናውቀዋለን። ሆኖም  በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀጥቃጭ ወይም የዕደ-ጥበብ አዋቂዎችና ነጋዴዎች እንደልዩ ፍጡር እንደሚታዩና እንደሚገለሉ ሁሉ፣ የእስላም ሃማኖት ተከታዮችን የማግለል አዝማሚያ እንደነበር ይታወቃል።  ከዕደ-ጥበብ አዋቂውም ሆነ ከእስላሙ ዘንድ ማህበራዊ እንቅስቃሴም(Social Mobility)እንዳይኖር እገዳ እንደነበር ግልጽ ነው። ህብረተሰቡ እርስ በርስ እንዳይተሳሰር፣ እነዚህ እንደ ዝቀተኛ የህብረተሰብ ክፍል ተደርገው ከሚቆጠሩት ጋር መገናኘትም ሆነ መጋባት አይፈቀድም ነበር። ስለሆነም የሃሳብ መንሸራሸርና ልውውጥ እንዳይኖር አግዷል። ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዳይዳብር እንቅፋት ሆኗል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በአውሮፓው የጨለማው ዘመን ታሪክ ውስጥም የተስፋፋ እንደነበረና፣ በነፋስ ኃይል የሚደገፉ ውሃ ማመንጫና እህል መፍጫዎች እንደሰይጣን ስራ የሚቆጠርበትም ዘመን እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። በተጨማሪም በሃማኖት ሳቢያ የተነሳ በካቶሊክና በፕሮቴስታን የሃይማኖት ተከታዮች መሀከል ሰላሳ ዐመት የፈጀ ጦርነት በመካሄድ እስከ 1648 ዓ.ም ድረስ በአንዳንድ ቦታዎች ሁለት ሶስተኛውን የሚያክል ህዝብ ከጨረሰ በኋላ በመምህራን ጣልቃ ገብነትና፣ ነገሩ የሚያዋጣ አለመሆኑን ሲደረስበት ነው እንዲቆም የተደረገው። ከዚይ በኋላ ነው የአውሮፓው ማህበረሰብ መረጋጋትና ወደ ህብረ-ብሄር ግንባታ ማምራት የተቻለውና፣ የውስጥ ገበያ ማዳበርና ማስፋፋት የቻለው። ያም ሆነ ይህ የነገሮችን ሂደት ከጠቅላላው የህብረተሰብ አወቃቀርና ከህሊና-ንቃት መኖርና አለመኖር ጋር ማያያዝ ከቻልን የበለጠ ግንዛቤ ሊኖረን ይችላል። በተለይም በአገራችን ምድር ውስጥ የተሃድሶ አብዮት አለመኖርና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብር እንቅፋት መፈጠር የህብረተሰብአችንን አወቃቀር ግልጽ በሆነ የስር-ክፍፍል ላይ እንዳይመሰረት አግዶታል ማለት ይቻላል። በተለይም ከብዙ  ዐመታት ጀምሮ በሰፊው እየተጠና በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሚቀርበው ጥናት እንደሚያረጋግጠው ከግሪኩ ስልጣኔ ጋር ያለተዋወቁና፣ የመንፈስ የተሃድሶ አብዮት ያልተካሄደባቸው አገሮች ለሳይንስ ዕድገት የማያመቹና ራስን ለመ ለሳጠየቅ እንደማይችሉ ነው። ስለሆነም ስለ አገራችን የሃይማኖት ጉዳይ በምንጽፍበት ወይም በምናወራበት ጊዜ እንዲያው ነገሩን በጥቁርና በነጭ መሀከል ያለ አስመስሎ መሳል ሳይሆን በሰፊው ማየት የቻልን እንደሆን ከስሜታዊነት ይልቅ የሰከነ ውይይት በማካሄድ ለገጠመን ችግር መፍትሄ መስጠት እንችላለን።

       ቀደም ብሎ በህውሃት ወይም በኢህአዴግ አገዛዝ ይካሄድ የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት አገዛዙ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሆን ብሎ  መጫወት የጀመረው ፖለቲካ ለሳይንስና ለጥበብ፣ እንዲሁም ለፍልስፍናና ለባህላዊ ዕድገት አመቺ ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ይበልጥ ሃይማኖታዊና በጎሳ ላይ ያተኮረ መነታረኪያና የእርስ በርስ ግጭት መፍጠሪያ መድረክ ነው ያመቻቸው። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ የክርስቲያኑን ሃይማኖትና የአማራውን የበላይነት ለማዳከም በሚል ካለምንም የከተማ ዕቅድ እዚህና እዚያ የተሰሩት መስጊዶችና እንደ አሸን መፍለቅ የጀመሩት የፕሮቴስታንት ወይም የፔንጤ ቆንጤ ሃይማኖት ተከታዮች በኦርቶዶክስ ክርስቲያኑ የሃይማኖት ተከታይ ዘንድ ፉክክርን በማስከተል የቤተ-ክርስቲያን ግንባታ ጥድፊያ መካሄድ ጀመረ። እንደነ አላሙዲን የመሳሰሉት በምንም ረገድ የሃይማኖት ዕምነት የሌላቸው እጅግ አደገኛ ሰዎች ከሳውዲ አረብያ ጋር ያላቸውን መቆላለፍና የገንዘብ ድጋፍ ተገን በማድረግ፣ እንዲሁም ከአገዛዙ ጋር ያለውን የሙስናና የማባለግ ግኑኝነት በመጠቀም ሰላማዊ ዜጋ በሆነው በኢትዮጵያዊው የሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅራኔ እንዲፈጠር ማድረግ ቻለ። በዚህ ዐይነቱ የተንኮል ስራ ውስጥ በተለይም በዘይት የናጠጡ በምንም መልኩ የዕምነት ተከታዮች ያልሆኑት የሳውዲ መሪዎች እርኩስ ተልዕኮአችውን ለመወጣት ያላደረጉትና የማያደርጉት ነገር የለም። እንደ ግብጹ፣ ቱኔዚያውና እንደናይጀሪያው ሁኔታ ስልጣን ለመያዝ ካልተቻለ እንኳ ብጥብጥ እንዲመጣ የማያደርጉት ነገር እንደሌለ አንዳንድ ፍንጮች ያመልክታሉ። በተለይም አሁን በየአገሮች ውስጥ በሰፈነው የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ቀውስ በመጠቀም ወጣቶችን ለመመልመል እንደሚችሉና እንደሚያሳስቱ በግልጽ የታወቀ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተረፈ፣ ሰለጠንኩኝ የሚለው በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም፣ እንደነ ኩዛኑስ፣ ላይብኒዝ፣ ካንትና ሺለር፣ እንዲሁም ሌሎች ታላላቅ ፈላስፎች የፈለሰፉትን የስልጣኔ ፈለግ በማዛባትና፣ በየአገሮች ውስጥ ጣልቃ አለመግባትን የሚያስተምረውን የካንትን የፍልስፍናና የፖለቲካ ትምህርት በመጣስ፣ አይ በነፃ ንግድ፣ ካሊያም በጎሳና በሃይማኖት በመግባት ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች በጦርነት እየታመሱ እንዲኖሩ በማድረግ ላይ እንዳለ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። ለዚህ ደግሞ ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የወታደር፣ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች ስልጠና፣ መመሪያውና „ዕውቀቱ“ ከምዕራቡ ዓለም የመጣ በመሆኑ፣ እምብዛም የፖለቲካ ጥበብ ያልተዋሃደው የሶስተኛው ዓለም ፖለቲከኛና የቢሮክራሲ ኃይል የየመንግስታቱን መኪና(State Machinery) ክፍት በማድረግ አገሮችን መቀመቅ ውስጥ እየከተታቸው ነው። የስልጣኔውን ፈለግ እያጨለመባቸው ነው። ዛሬ እንደነ ኢራቅና ናይጄሪያ የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ በሃይማኖት ስም ተሳበው የሚካሄዱት ጭፍን ሰው ግድያዎች የፀጥታ ኃይሎችም እንዳሉበት ይነገራል። አንዳንዶች በማስረጃ የተደገፉ ጥናቶችን ያቀርባሉ። በሳውዲ አረብያና በአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት መሀከል የጠበቀ ግኑኝነትና የኢንፎርሜሽን ልውውጥ እንዳለ አሁን በቅርቡ ደር ሽፒግል የሚባለው በጀርመን በብዛት በምሁራን ዘንድ የሚነበበው ሳምንታዊ መጽሄትና፣ የየቀኑ የድህረ-ገጽ ዘገባ በይፋ አውጥቷል።

       ሃቁ ይህ ከሆነ በኢትዮጵያችን ላይ እንደ አገዛዝ ሃያ ሰባት ዐመት ያህል ኢገዛ የነበረው ኃይል ይህ ዓለም አቀፋዊ የተወሳሰበ የፖለቲካ ሁኔታና አሻጥር ገብቶት ነበር ወይ?  ገብቶስ ከነበር ለምን በሃይማኖት ውስጥ እየገባ አዳዲስ ቅራኔ በመፍጠር ህብረተሰብአችን የባሰውኑ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ለማድረግ በቃ? በዚህ ዐይነቱ ጥበብ የጎደለውና በተንኮል የተሞላ ፖለቲካው ምንስ ጥቅም ያገኛል? ቢያንስ ለጠቅላላው ኢትዮጵያ እንኳ ባያስብ፣  ለምንስ ለወደፊቱ የልጅ ልጆቹ ዕድል አያስብም? ምን ዐይነትስ ኢትዮጵያን ጥሎ ለማለፍ ነው ይመኝ የነበረው ?  በጦርነት እየታመሰች የሚኖርባትንና አቅጣጫው የጠፈባትን ህዝብ ጥሎ ማለፍ ነበር ወይ የአገዛዙ ዓላማ?  በዕውነቱ   ዐመታት ያህል ኢትዮጵያን ሲያምሳት የነበረው የህውአት አገዛዝ የሚያደርገውን ነገር የሚያውቅ አልነበረም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የዛሬው በዶ/ር አቢይ የሚገዛው አገዛዝ ይህን ያህልም ከህውሃቱ የጥፋት ፖለቲካ የተማረ አይመስለኝም። የነገሩን ውስብስብነትና አደገኛነት በደንብ የተገነዘበ አይመስልም። በአገራችን ምድር አንድ ዐይነት ውዝግብ ቢፈጠር ማንኛውም ኃይል ሊያመልጥ አይችልም። የሚመሽግበት ቦታ ሊኖር አይችልም። ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን ጥሎ መሄድ ሊሆን ይችላል። በሌላ ወገን ደግሞ የዓለም ሁኔታ በተለይም አሜሪካ አመቺ እንዳለሆነ መገንዘብ ያስፈልግፋል። በአጭሩ ነገሮች ሁሉ እየጠበቡ እንጂ እየተሻሻሉና አመቺ እየሆኑ በመምጣት ላይ አይደሉም። በተጨማሪም የትግሪም ጎሳ ሆነ ሌሎች ጎሳዎች እንደኦሮሞ የመሳሰሉት በማይገረሰስ ግንብ ተከልለው የሚኖሩ አይደሉም። በሌላ አነጋገር አንድ ቦታ እሳት ከተቀጣጠለ  ጠቅላላውን አገሪቱን የማዳረሱ ኃይል ከፍተኛ ነው።  ሁሉንም ስለሚያጋይ የትግሬውም ሆነ የኦሮሞው እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እጣ የተለየ ሊሆን አይችልም። የተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚፈጠረው ውዝግብና ችግር ወደዚያም ሁሉም ቦታ ይዛመታል። ትግሬ ውስጥም የሚፈጠረው እንደዚሁ ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ይተላለፈል። እንደምናየው በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገሮች የሚፈጠሩትና የሚሰራባቸው መጥፎ ባህሎች ወደኛም በመሸጋገር እያዋከቡንና እሴታችንን እንድናጣ እያደረጉን ነው። ስለዚህም ትግሬዎች እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፣ ሰውና ምንም ነገር በማይደርስበት ደሴት ውስጥ ይኖሩ ይመስል በተሳሳተ ፖለቲካ በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚፈጸመው ግፍ ለሁላችንም የሚተርፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፍገልጋል።

       በሌላ ወገን ግን ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖትን አሳቦ የተነሳው የመብት ጥያቄና ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም እንቅስቃሴ ፈሩን እስካልያዘ ድረስ መደገፍ ያለበት ነው። በዚህ የመብት ጥያቄ ውስጥ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተገንዝበው ሁኔታው ከቁጥጥር እንዳይወጣ ማስተማር አለባቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖትም ሆነ በሌላ መስክ የሚከሰት ውዝግብም ሆነ ብጥብጥ ለማንም የሚጠቅም አይደለም። ሃይማኖት ህብረተሰብን ለመያዝና እሴትንና ስነ-ምግባርን ለማስተማር እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ያህል፣ አንድ ህዝብ እየተራበና እየተሰደደ፣ እንዲሁም በድንቁርና ዓለም ውስጥ እየኖረ ሃይማኖትን ብቻ ተከተል ቢባል ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የረሃብና የድንቁርና፣ እንዲሁም የኋላ-ቀርነት ሁኔታ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጥያቄዎች ናቸው። አንድ ህዝብ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚያመቸው ዕውቀት ከሌለው የቀን ተቀንና ዘላቂውንም ችግር ሊፈታ አይችልም። እንዲሁም የተረጋጋና፣ ሁሉም በየፊናው ዕምነቱን የሚያካሄድበትን ህብረተሰብ ሊመሰርት አይችልም። ስለሆነም ሁሉም ሃይማኖቶች ሃይማኖትን ከሌሎች የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ጋር ማያያዝ መቻል አለባቸው። አንድ ህዝብ እየተራበና እየተጠማ፣ እንዲሁም መጠለያ አጥቶ በየቦታው የሚወድቅ ከሆነ ሃይማኖት ማቴሪያላዊ ፍላጎቶችን ሊያሟላለት በፍጹም አይችልም።

                                    የፓለቲካ ጥያቄ!

         በአገራችንና በታሪካችን ውስጥ ሰፋ ያለ ከፍልስፍና ጋር የተያያዘ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩና፣ የተለመደም ስላልነበር ብዞዎቻችን የፖለቲካን ትርጉም አይ ከአመጽ ጋር ወይም ደግሞ ከአሻጥር ጋር በማያያዝ ስልጣን ለመያዝ እንታገላለን። ቀደም ብሎም ሆነ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተዘረጋው ትምህርት ጭንቅላትን የሚያድስና የአስተሳሰብን አድማስ የሚያሰፋ ስላልነበር በአገራችን ታሪክ በሳል የሆነ አመራርም ሆነ በስነ-ስርዓት የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ሊፈጠር አልቻለም። እንዲሁም ከበርቴያዊ መደብ መፈጠር ባለመቻሉ ስርዓቱን ለመጋፋትና በምትኩ የተሻለ ህብረተሰብ ለመመስረት አልተቻለም። በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ በመጠኑም ቢሆን ፖለቲካ ታሪክ መስሪያና ህብረተሰብ መገንቢያ መሳሪያ መሆን የቻለው አውሮፕያውን ከኛ የበለጡና በአፈጣጣራቸው ኢንተለጀንት ስለነበሩ ሳይሆን በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን ዕውቀት በማዳበርና በማስፋፋት የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት ለመጣል በመቻላቸው ነው። ከአስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እየዳበረ የመጣው የስራ ክፍፍልና የንግድ እንቅስቃሴ የግዴታ በአገዛዞች ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማሳደር ቻለ። አዲሱ የህብረተሰብ ክፍል ራሱ የባህል እንቅስቃሴ በማድረግና ከተማዎችን በመገንባት የፊዩዳሉን ሀብረተሰብ መጋፈጥና ስልጣንም ተቀናቃኝ ወደመሆን በቃ። በተጨማሪም አዳዲስ ፈላስፎችና አዋቂዎች ሲፈጠሩ፣ ትምህርታቸውና ትግላቸው ህብረተሰባዊ ዕድገትና የፖለቲካ አወቃቀር አንድ ላይ መጣመር እንዳለባቸው በመረዳት፣ የተበላሸ የፖለቲካ ሁኔታ ባለበት አገር ውስጥ አንድን አገር በፍጹም መገንባትና ሰላም ማጎናጸፍ እንደማይቻል በመገንዘብ ሰፋ ያለ ምርምር ጀመሩ። የጽሁፍ መኪና በጉተንበርግ አማካይነት ሲፈጠር እንደመጽሀፍ ቅዱስንና እንደ ፍልስፍና፣ እንዲሁም የሳይንስ ምርምሮችን እያባዙ ለማሰራጨት በጣም ቀለላቸው። በዚህ ላይ በጊዜው ብቅ ያሉት የአውሮፓው ምሁራን ዕውቀቶቻቸውን ለማጣመርና፣ እየተራረሙ በአንድ ላይ ለመታገል የሚጥሩ ነበሩ። አንደኛው ሌላውን ለማጥፋትና በመናቅ ዕውቀት እንዳይስፋፋ ተንኮል የሚሸርብ አልነበረም። ምርምሮቻቸውን ለተመለከተ ከተንኮል የፀዱ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ፍጹም በሆነ የመንፈሳዊና የምርምር ዓለም ውስጥ ስለነበሩና መፍጠርም ስለቻሉ ዛሬ የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በሙሉ መሰረታቸውን ጥለውን አልፈዋል። ለስልጣኔ ብለው ታጥቀው ባይነሱና ህይወታቸውን ባይሰዉ ኖሮና፣ ሀቁን ከውሸቱ እየነጠሉ ብርሃንን ባያሳዩን ኖሮ እንደ እንስሳት በጫካ ውስጥ የምንኖር ነበር። ስለሆነም የሳይንስ ምርምር በፖለቲካ ሂደትና የኃይል አሰላለፍ ላይ ተፅዕኖውን በማሳደር መንግስታት ፖለቲካቸውን እንዲያርሙ አስገድዷቸዋል ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና በምንም ተነጣጥለው እንደማይሄዱ፣ ፖለቲካም ሲባል በስነ-ምግባርና ሞራል መታቀፍ እንዳለበት፣ ስነ-ምግባርና ሞራል የጎደለው ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት እንደሚያጨናግፍና ወደ ውዝግብም እንደሚያመራ ነው የተደረሰበት። የፕላቶን የፖለቲካና የፍልስፍና ስራዎች ሙሉ በሙሉ ስነ-ምግባራዊ ናቸው። የአርስቲቶለስም ስራ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። በሌላ አነጋገር፣ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ፖለቲካ ከፍተኛውን ቦታ ስለሚይዝ ለማንም ወሮበላ የሚሰጥ፣ ወይም ማንም በፖለቲካ ስም እዚህና እዚያ የሚለፍፍ የሚያካሂደው ነገር ሳይሆን በአዋቂዎችና በብልሆች መካሄድ ያለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የአንድ ህብረተሰብና የአንድ አገር ጉዳይና ዕድል ፖለቲካ ነኝ በሚሉ እጅ የተያዘ ስለሆነ በአቦ-ሰጡኝ ወይም በብልጣብልጥነት የሚካሄድ አይደለም። ለዚህ ነው ፕሮፌሰር ካርል ፖፐር ግልጽ ህብረተሰብ(The Open Society) በሚለው ግሩምና አንዳንድ ቦታ ላይ አወዛጋቢ መጽሃፋቸው ውስጥ ስለ ፖለቲካና ስለፖለቲካል እንጂነሪንግ አስፈላጊነትና፣ በተለይም ደግሞ ለዲሞክራሲና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ውስጥ የተለያዩ ኃይሎች ይህንንም ወይም ያንን ትርጉም በመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ የሚያሰተምሩት። በመሆኑም፣ በአውሮፓ ውስጥ ከብዙ መቶ ዐመታት የምሁራዊ ሂደት፣ ግጭትና እንዲሁም ልምድ በኋላ መቻቻልና መግባባት፣ እንዲሁም መቀላለድ፣ አንዳንዴም በካባሬት መልክ ማሾፍ እንደባህል ሆኖ መወሰድ የተለመደው የአውሮፓው ህብረተሰብ መንፈሱ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በልዩ ልዩ ነገሮች ስለታነፀ ነው።  በሌላ ወገን ግን እንደ አገራችን ባሉ አሁንም ቢሆን በፊዩዳል ኖርሞች በተተበተቡ ህብረተሰቦች ውስጥ ለፖለቲካ ነጻነት የሚደረገው ትግልና ደፈር ብሎ ለመናገር አለመቻል፣ ፓለቲካን እንደ ሳይንስ ሳይሆን እንደ አሻጥር መስሪያነት መሳሪያ የሚታየውና መገዳደያም ሊሆን የበቃው ምሁራዊ ኃይላችን በጣም ደካማ ስለሆነ ነው። በተለያዩ ነገሮች በሚገለጹ የታነፅንና ሶሻላይዝድ ያልሆን በመሆናችን ከፍተኛ አለመተማመን አለ፤ የሃሳብ ግልጽነትና ነገሮችን በቀላሉ ለማየትና ለማስረዳት እንዳንችል ታግደናል። ሺለር ዓለም አቀፋዊ ታሪክ ማለት ምን ማለት ነው? ለምንስ የዓለም አቀፍ ታሪክን መማር አለብን ?  በሚለው ግሩም ስራው ውስጥ የሚያሳስበን የሰው ልጅ ሶሻላይዘድ ለመሆን ብዙ መቶ ዐመታት እንደተጓዘና መጓዝም እንዳለበት፣ በዚህም መልክ ብቻ ቀስ በቀስ ራሱን በማግኘት ታሪክ መስራት እንደሚችል ነው። በዚሁ ስራው ውስጥ በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን የአውሮፓውን ችግር በሰፊው ካጠናና በድራማ መልክ ከቀረፀ በኋላ፣ ከአርስቲቶለስ ጀምሮ ስለ ዲሞክራሲ ብዙ ብዙ ሰምታናል፣ አሁንም ቢሆን ከአረመኔያዊ ባህሪያችን አልተላቀቅንም በማለት የሰውን ልጅ የመሰልጠን ችግር ይጠቁመናል። ስለሆነም ስለዲሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ግንባታ ስናወራ እስከዛሬ ከምናደርገው ትግል አንድና ሁለት እርምጃዎች ቀደም ብለን መሄድ አለብን። ታሪካችንን ወደ ኋላ ተመልሰን መመርመር አለብን። የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ እያለን ዛሬ ለምን በእንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ላይ ለመገኘት ተገደድን? ብለን መጠየቅ አለብን። ከዚህም በሻጋር የህብረተሰብአችንን ታሪክና ዕድገት በሌሎች የህብረተሰብ ዕድገቶች መነፅር ለመመልከት መሞከር አለብን። ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው ለተወሳሰበው የአገራችን ችግሮቻችን በመጠኑም ቢሆን መልስ መስጠት የምንችለው።

         ቢያንስ አብዮት ፈንድቶ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገባን ቢባልም፣ በተማሪው ጊዜ የነበረው ግልጽ ያልሆነ፣ በአብዛኛው መልኩ ወደ አንድ ወገን የሚያደላና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ የጎደለው ትግል ስልጣን ላይ ባሉትም ሆነ ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ዘንድ ሲንጸባረቅ ይታያል። ምክንያቱም ፖለቲካ የሚለው ግዙፍ ጥያቄ ወደ ስልጣን መያዣነት ተቀንሶ ሰለሚታይና፣ ሰፋ ያለው የህብረተሰብ ጥያቄ፣ ለምሳሌ የባህል ተሃድሶ፣ የማህበራዊ ጉዳይና የህብረተሰብ ግንባታ ጉዳይ፣ የኢኮኖሚና የእሴት ጉዳይ፣ እንዲሁም ደግሞ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይ ምንም ቦታ ሳይሰጣቸው ስለሚቀር ሰፋ ላለ ምሁራዊ ውይይት በሩ ተዘግቷል። ዛሬም ያለው ችግር ይህ ነው። እንደምሰማው ከሆነ ቀድሞ በአፄው አገዛዝ ዘመን ከፖለቲካ ውጭ ስለሌላ ነገር ማሰብ አይቻልም ነበር። ሁሉም አብዮተኛ በነበረበት ወቅት የፖለቲካ ትግሉ ከስልጣን ተሻግሮ የሚሄድ አልነበረም። ምክንያቱም ቀላል ነው፤ ሁሉም ነገር ከስልጣን መያዝ በኋላ መፈታት የሚችል ነው ነበር መልሱ። በደርግና በኢህአዴግም ዘመን ይደረግ የነበረውና የሚደረገው እንቅስቃሴ ፖለቲካ ከስልጣን ጋር ከመያያዝ ተነጥሎ አይታይም ነበር፤ አይታይምም። ዛሬም „በለውጥ ዘመን“ ያለው  ችግር ይህ ነው። ነገሮችን በሰፊው አለመመልከትና በትናንሽ ነገሮች መደሰትና መዝናናት።  በዚህም ምክንያት ስልጣን ላይ ያለው ስልጣኑን ላለመልቀቅ ሲል ከዚህ ወይም ከዚያኛው ኃያል መንግስት ጋር በማበርና፣ የማይሆን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል የተወሳሰቡ ችግሮችን በመፍጠር ወደ ፍጥጫ ያመራል። ይህ ዐይነቱ ፖለቲካን የስልጣንና የተንኮል መስሪያ መሳሪያ አድርጎ የመቁጠሩ ጉዳይ በጭንቅላታችን ውስጥ ተቋጥሮ እስከቀረ ድረስ ህብረተሰብአችን ዘለዓለሙን እየታመሰ ይኖራል። ስለሆነም ድሮ ታጋይ ነበርን በሚሉትና አሁንም እንታገላለን በሚሉት ዘንድ ሀቀኝነት የጎደለው ትግል የሚካሄደው ፓለቲካ የሚባለው ግዙፍና ሳይንሳዊ መሳሪያ ከህብረተሰብአዊ እሴትና ከፍልስፍና ውጭ ተነጥሎ ስለሚታይ ነው። ለምሳሌ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የተካፈሉት ታጋዮች በሙሉና ደርግንም ጨምሮ አንድም ቦታ ላይ ስህተት እንዳልሰሩ ነው የሚነግሩን። ሁሉም ስህተት አልሰራሁም፣ ለጥፋቱ ተጠያቂ አይደለሁም፣ በቦታውም አልነበርኩም የሚል ከሆነ ታዲያ ዛሬ ውድ ኢትዮጵያችን እንደዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪና አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ ለምን ለመውደቅ ቻለች? ተጠያቂው እኛ ካልሆን ማን ሊጠየቅ ነው? እግዚአብሄርና አባቶቻችን ወይም የማናውቀው ይህንን ወይም ያንን አድርጉ የሚለን የረቀቀ ኃይል ወይም ሰይጣን ነው ሲጠመዝዘን የነበረው? አንድ ከሰማይ ላይ ዱብ የሚል ነገር፣ ወይም የመሬት መንቀጥቀጥና የውሃ ሙላት፣ ወይም ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ካልሆነ በስተቀር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚደርሱ መመሰቃቀሎች፣ ጦርነትና ረሃብ ወይም ድህነት፣ እንዲሁም በሽታ የሰው ልጅ ያላዋቂነት ውጤቶች ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ የሰውን ልጅ የስልጣኔ ታሪክ ስንመለከት፣ ከዛፍ ላይ መንጠልጠልና፣ በአደንና ፍራፍሬ እየለቀሙ መኖር፣ ከዚያ በኋላ በመቀመጥና ወደ እርሻ ተግባር በመሰማራት አዲስ ህይወት መፍጠርና፣ ቀስ በቀስም የተወሳሰበ የስራ ክፍፍል መፍጠር የሰው ልጅ ሰላም ካገኘና የማሰብ ኃይሉንም ከተጠቀመ ተዓምር መስራት እንደሚችል ነው የምንገነዘበው። በሌላ አነጋገር፣ በማንኛውም የተለያየ አመለካከትና የአሰራር ስልት በሚከተሉ ምሁራን ጥናት እንደተደረሰበት የሰው ልጅ ከፈለገ ከምንም ተነስቶ ስልጣኔዎችን እንደሚገነባ ነው። ለዚህ ደግሞ የግሪክ ፈላስፎች ፍላጎት(Will) የሚሉት ከፍተኛ ትርጉም ያለው ፅንሰ-ሃሳብ አለ። ይህ በጎደለበትና የማሰብ ኃይል በተዳከመበት፣ ከዚህም ባሻገር ፖለቲካ ከፍልስፍና ተላቆ ወደ ንጽሁ ስልጣን መያዣነት በሚቀየርበት ዓለም ውስጥ ህብረተሰቦች ዘለዓለማቸውን እየተወዛገቡ ይኖራሉ።

        ወደ ኢህአዴጉ ወይም የህውሃቱና የዛሬው የዶ/ር አቢይ ፖለቲካ ስንመጣ፣ ሰዎቹ የፊዩዳሊቱና የተዘበራረቀው ካፒታሊዝም(Peripherie Capitalism)ውጤቶች እንደመሆናቸው መጠን የተለየ ፖለቲካ ሊያካሂዱ  የሚችሉ አልነበሩም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት ያካበቱት ሀብት ጋር ተጨምሮ ፖለቲካን የሚረዱት ስልጣንን ከመያዝ ባሻገር ሊሆን አይችልም። በሌላ ወገን ደግሞ እንደወትሮው በህብረተሰብአችን ውስጥ ምሁራዊ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሊገለጽ የሚችል እንቅስቃሴ ሊዳብር ባለመቻሉ በነዚህ ሰዎች ላይ ምሁራዊ ግፊት ማድረግ አልተቻለም። በመግቢያው ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የፖለቲካ መድረኩ ክፍት እየሆነ የመጣውና ቀስ በቀስም ለአዳዲስ ኃይሎች መልቀቅ የተገደደው በሳይንስና በፍልስፍና፣ በተፈጠረው የምርት ኃይሎች ዕድገትና በተወሳሰበ የስራ ክፍፍልና የንግድ ልውውጥ አማካይነት ግፊት ብቻ ነው። እንዲያው በምርጫ በመወዳደርና፣ በምርጫ እንካፈል፣ ወይም ስልጣን አካፍለን በማለት አይደለም። ወይም ደግሞ ስልጣን ለመውጣት ሲባል የውጭን ኃይል በመለማመጥና አስታርቁኝ በማለት አይደለም። ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊመጣ የቻለውና የሚችለው በድሮው ስርዓት መኖር አንፈልግም፣ የድሮው ስርዓት ፀረ-ዕድገትና አቆርቋዥ ነው፣ የሰውን የመፍጠር ኃይል ያፍናል  ብለው በተነሱ ኃይሎች አማካይነት ብቻ ነው። በአውሮፓ ውስጥ የፊዩዳሉን ስርዓት መፈረካከስና የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመለከት፣ የአረጀው ስርዓት ከየአቅጣጫው የተወጠረና መፈናፈኛ ማግኘት ያልቻለ ስለነበር ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ለኢንዱስትሪ አብዮት መካሄድ መንገዱን እንዲለቅ ተገዷል። በመሆኑም የፔሪ አንደርሰን የፍጹም ሞናርኪዎች ግሩም መጽሀፍና የፖላንዛስን መጽሃፎችን ላነበበ፣ የማርጋሬት ያኮብን የሳይንስ ባህልና የምዕራብ አውሮፓን የኢንዱስትሪ አብዮት ታሪክ ስናነብ፣(Scientific Culture and the Making of the Industrial West)፣ወይም ደግሞ የዲይከስተርሁስን(Dijksterhuis) ወደ መካኒክነት የተለወጠችው ዓለም(The Mechanization of the World) የሚለውን መጽሀፍ ስናነብ መገንዘብ የምንችለው ሁኔታዎች ሲለወጡ የግዴታ አገዛዞችም ሳይወዱ በግድ ቦታውን ይለቃሉ። በድሮውና በአረጀው አገዛዝ መግዛት ስለማይችሉ የግዴታ ወደ መገፍተርነት ያመራሉ። የግዴታ ውስጥ-ኃሉ ከፍ ያለና ለአዳዲስ ሃስቦች አመቺ የሆነ ስርዓት ይፈጠራል።

        ዛሬ በአገራችንም ሆነ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ያለው ችግር በስልጣን ላይ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ፣ አንዳንድ ካልሆነ በስተቀር የፖለቲካን ጥያቄ ስልጣን ከመያዝና በቀላሉ ዝናን ከመጎናፀፍ ባሻገር ማየት የማይችሉ ናቸው። በመሆኑም ለፖለቲካ ስልጣንና ለፖለቲካ እንታገላለን የሚሉ ፓርቲዎች ሰፋ ያለውን የምሁር እንቅስቃሴ እርግፍ አድርገው በመተውና ፓለቲካን ከሳይንስ ጋር ለማገናኘት ስለማይፈልጉና ጥረትም ስለማያደርጉ፣ ዛሬ እንደምናየው የፖለቲካ ስልጣን ድንቁርናን በተካበቱ ሰዎች እጅ ወድቆ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ሲሰቃዩ እናያለን። ለዚህም ነው በቀላሉ የአፍሪካ መንግስታት በየአገሮቻቸው ውስጥ የተትረፈረፈ ሀብትም እያለ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ፣ እንዲሁም እንቬስተር ነን በሚሉ በመታለል ሀብት እንዲበዘበዝና ህብረተሰቦቻቸው ተዘበራርቀው ወደድህነት እንዲያመሩ የሚደረገው። ህብረተሰብአዊና ማሀበራዊ ኃላፊነት(Social awareness)፣ እንዲሁም የተፈጥሮን ህግጋትና ለሰው ልጅ የምትለግሰውን ከውሃ እስከ አየር፣ ከአዕፅዋት እስከ ልዩ ልዩ ነገሮች ድረስ  በጭፍን የሚበዘበዘውና፣  በተፈጥሮና በአካባቢ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ የሚያረጋግጠው አፍሪካ የቱን ያህል ስለ ሰውልጅ ምንነትና ስለተፈጥሮ ህግ ባልገባቸው መሪዎች እንደምተዳደር ነው። አብዛኛወ የአፍሪካ አገሮች፣ ኢትዮጵያችንም ጨምሮ የአገር ምንነት ባልገባቸውና የአገርን ጥቅም(National Interest) ማስጠበቅ በማይችሉ አገዛዞች የሚተዳደሩ ናቸው። ከዚህ ስንነሳ የአፍሪካን መሪዎች የህሊና አወቃቀርና ፖለቲካ መረዳት የምንችለው እንዲያው አምባገነኖች ናቸው፣ ለዲሞክራሲ መፈናፈኛ የማይሰጡ ናቸው በሚል ሳይሆን- ይህ ዐይነቱ የተደጋገመ አባባል ሳይንሳዊ አይደለም ጠቅላላውን የህብረተሰብ አወቃቀር በየኢፖኩ ወስደን መመርመር የቻልን እንደሆንና፣ የምርት ኃይሎችን ዕድገት ከግንዛቤ ውስጥ ያካተትን እንደሆን ብቻ ነው።

       ስለዚህም በኢትየጵያ ውስጥም ሆነ ከውጭ ሆኖ የሚደረገው የፖለቲካ ትግል ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እስካልያዘና፣ ግልጽና ድፍረት የተሞላበት፣ ግን ደግሞ ከወገናዊነት ነፃ የሆነ ትግል እስካልተካሄደ ድረሰ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣኔ ጥሙ ለብዙ መቶ ዐመታት ተንጠልጥሎ እንደሚቀር ካሁኑ መናገር ይቻላል። ስለዚህም የዛሬው አገዛዘም ሆነ ማንኛውም ለፖለቲካ እታገላለሁ የሚል ሁሉ በጠብመንጃ ታግዞ ረግጬ እገዛለሁ የሚል ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠፋፋት ነው የምንጓዘው። የፖለቲካ ጥያቄ ከቂም በቀልነትና፣ ድሮ እንደዚህ አድርገኸኝ ነበር፣ እኔም በተራዬ አሳይሃለሁ በሚል የሚፈታና መስመር የሚይዝ ጉዳይ አይደለም። የፖለቲካ ትግልና ለስልጣን የሚደረገው ጉዞ ከግለሰብ ፍላጎትና ከስልጣን ስግብግብነት ባሻገር መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ፖለቲካ ግልጽ የሆነ ውይይትንና ክርክርን ይፈልጋል። ክርክር በማይደረግበት፣ ጥቂቶች በእግዚአብሄር እንደተመረጡ በሚቆጠሩበት፣ እነሱ የሚሰነዝሩትን ከሳይንስ ውጭ የሆነ አነጋገርና አጻጻፍ የተቸ ሁሉ የሚሰደብበትና የሚሳደድበት ከሆነ ፖለቲካ ሳይንሳዊ ትርጉም ያለው ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ መሆኑ ቀርቶ ወደ መፋለሚያ በማምራት ህብረተሰብ እንደሚመሰቃቀል ያደርጋል። ስለዚህም ነው ደጋግሜ እንደምለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጋጠ-ወጥነት ባህርይው እስካልተላቀቀ ድረስና፣ በከፍተኛ ደረጃ በፍልስፍናና በስነ-ምግባር እስካለተካሄደ ድረስ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንደ አገርና እንደ ህብረተሰብ መኖር አትችልም። ማንም የሚረባረብባት አገር በመሆን ህዝቦቿ እየተሰደዱና እየተረገጡ ይኖራሉ ማለት ነው። ይህንን ዐይነቱን ውርደት ለህዝቡና ለልጅ ልጆቹና ለአገሩ የሚመኘው ማነው?  ተንኮለኛ ካልሆነ በስተቀር፣ በድንቁርና  ዓለም ተውጦ የሰውን ስም በሆነው ባልሆነው ከሚያጠፋው በስተቀር፣ ማንኛውም በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረና እግዚአብሄርን እፈራላሁ የሚል በሙሉ የሚከተለው ርኩስ ተግባር አይደለም።

         ይህ ብቻ አይደለም አስቸጋሪው ጉዞአችን።  በአሁኑ ዘመን እንደምናየው በብዙ አገሮች ፓለቲካ የችግር መፍቻ መሳሪያ መሆኑ ቀርቶ ይህንና ወይም ያኛውን ርዕዮተ-ዓለም እናራምዳለን የሚሉ ፓርቲዎች በመፍጠር፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ኃያል መንግስትና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው አፈ-ቀላጤዎች በመሆን ህብረተሰቦች የሚዘበራረቁበት መድርክ ሆኗል። ስልጣን ላይ የወጡ፣ እኔ ሊበራል ነኝ፣ ኮንሰራቪቲብ ነኝ፣ ሶሻል ዲሞክራት ነኝ በማለት ከህገ-መንግስቶቻቸው ውጭ የሆነ የኢኮኖሚና የሶሻል ፖሊሲ በማካሄድ ከውስጥ ህብረተሰቦች በውዝግብ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ እያደረጉ ነው። በእኛ አገርም ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎች አሉ። በደንብ የመደራጀታቸውንና ርዕይታቸውን የመመርመሩን ጉዳይ  ወደ ጎን ትተን፣ አንደኛ፣ ይህ ሁሉ ፓርቲ ለምን ያስፈልጋል ? በሁለተኛ ደረጃ፣ እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች ለምን ዐይነቷ ኢትዮጵያና ለምንስ ዐይነት ህብረተሰብ ነው የሚታገሉት? ሶስተኛ፣ ስልጣን ቢይዟ እንኳ እንዴት አድርገው ነው ሰፋ ያለ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ሊገነቡ የሚችሉት? ብለን ጥያቄ ብናቀርብ በቀላሉ መልስ የምናገኝ አይመስለኝም። እነዚህ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ሆነ ወደፊት በጨለማ ዓለም ውስጥ እንደሚኖር ከአሁኑ መተንበይ ይቻላል።

አስቸጋሪው የህብረተሰብ ጥያቄ ጉዳይ!

              ከዚህ ቀደም ባወጣሁት መጣጥፌዎች ላይ ስለህብረተስብ ምንንት በመጠኑም ቢሆን አብራርቻለሁ። አሁን ደግሞ በህብረተሰብና በሃይማኖት መሀከል ያለውን አስቸጋሪ ግኑኝነት ለማሳየት እሞክራለሁ። ላይ አንዳልኩት ፍልስፍና ከሃይማኖት ጋር ሲወዳደር ረዘም ያለ የብዙ መቶ ዐመታት ዕድሜ ቢኖረውም፣ ከፍልስፍና ይልቅ የሰውን ልጅ በሃይማኖት መማረኩ እጅግ ቀላል ነው። አንድንዶች እንደሚሉት ከሆነ የሰው ልጅ ብዙ መጨነቅ ስለማይፈልግ በቀላሉ ወድ ዕምነት ያመራል። ይሁንና በምዕራብ አውሮፓ ታሪክ ውስጥ ፍልስፍናና ሃይማኖትን ለማዛመድ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የተሳካ ቢሆንም፣ ይህ ጉዳይ ግን በካፒታሊዝም ልቅ ያጣ የፍጆታ አጠቃቀምና የአኗኗር ስልት እየላላ ሊመጣ ችሏል። የፍጆታ አጠቃቀምና ከፍተኛ የስራ ጭነት ተደምረው፣ የፍጆታ አጠቃቀም ሃይማኖትን እየተካው በመምጣት ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያት የመንፈስ ቀውስ በመታየት ዘረኝነትና ልዩ ዐይነት አመጻዊ ድርጊቶች አልፎ አልፎ ይታያሉ። በሌላ ወገን በየቦታው የተስፋፋው የባህል መዝናኛ ቦታና የመጻሀፍት ቤቶች መስፋፋት ለህብረተሰብአዊ መረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋጻኦ እያደረጉ ነው። ወደኛ አገር ስንመጣም የሃይማኖት ጉዳይ ጠበቅ ብሎ የሚታይ ቢሆንም፣ ከቁጥጥር የወጣው የግሎባል ካፒታሊዝም መስፋፋትና ልዩ ልዩ ጥሩ ጥሩ የአገራችንን እሴቶችን የሚያዳክሙ ባህል ነክ ነገሮች መስፋፋት በህብረተሰብ ውስጥ ልዩ ዐይነት ቅራኔና የህብረተሰብ እሴት መላላት እየፈጠሩ ነው። ይህንን እርስበርሱ የተምታታ ሁኔታ ለመግታትና፣ በመንፈሳዊና በፍጆታ አጠቃቀም መሀከል ያለውን ግኑኝነት ሚዛናዊ ለማድረግ የሚችሉ ኢንስቲቱሽኖች ስለሌሉ የህብረተሰባችን ጉዞ ወዴት እንደሚያመራ በግልጽ መናገር አይቻልም። በየቦታው መጻህፍት ቤቶች ወይም የኳስ መጫዎቻዎችና ልዩ ልዩ የስፖርት ክለቦች፣ የቲያትር ቤቶችና ሙዝዬሞች እንዲሁም ጋርደኖች ስለሌሉ ወጣቱ ትውልድ አይ ጨአት ቃሚ ሆኗል፣ የተቀረው ደግሞ በዚኽኛው ወይም በዚያኛው ሃይማኖት በጠመድ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶታል።  ወጣቱን በልዩ ልዩ ማህበራዊ ነክ ነገሮች ለመያዝ የተደራጁ ማህበራት ስለሌሉ እያረጀ የመጣውን ትውልድ ሊተካ የሚችል ታታሪና ለአገር አሳቢ ትውልድ ለማፍራት አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህንን ዓላማ-ቢስ ኑሮ ለመግታት የሚችል በመንግስት በኩልም የሚወሰዱ እርምጃዎችም የሉም። ቻሎታ የማነስ ጉድይ ብቻ ሳይሆን የዛሬው አገዛዝ ፍላጎትም ያለው አይመስልም። ስለሆነም ከውጭ የሚመጡ የተለያየ ተልዕኮ ያላቸው ሃይማኖቶችም ወይም ሴክቶች በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ተፅዕኖ በማሳደር በህብረተሰብአችን ውስጥ ልዩ ዐይነት ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው።

     በተለይም ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ሌሎች የክርስቲያኑን ሃይማኖት የሚጋፉ ግን ደግም በክርስቶስ ስም የሚሰብኩ በመስፋፋትና የወጣቱን መንፈስ በመሰለብ በህብረተስብአችን ውስጥ ቅራኔ እንዲፈጠር አድርገዋል። የስራ ዕድል የሌለው ወደዚያ በመሰማራት የነዚህ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ሰለባ በመሆን ፈጣሪና የራሱን ዕድል ወሳኝ እንዳይሆን ተደርጓል። ይህ ዐይነቱ ወጣቱን ትውልድ የመሳብ ጉዳይ በብሄራዊ ነፃነትና በህብረተሰብ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው መናገር ይቻላል። በታሪክ እንደሚታየው አገሮችና ህብረተሰቦች የሚዳከሙትና ለውጭ ወረራ የሚጋለጡት በሃይማኖትም አማካይነት ነው። የዛሬው በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች መስፋፋት ስልጣኔን በየአገሮች ከማዳበርና ህብረተሰቦችን ከማዋቀር ጋር የተያያዘ አይደለም። ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊና የምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለባቸው አገሮች በሃይማኖት ተሳበው ግጭቶች ስለሚፈጠሩ እነሱን ለመቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። በአንድ ወቅት በሚክሲኮ ይታይ የነበረው የኢቫንጄሊስቶችና የካቶሊኮች የእርስ በርስ ግጭት የአሜሪካ  ኢቫንጄሊስቶች ባደረጉት ግፊት ነበር። ከዚህም ባሻገር የእስልምና ሃይማኖት በተለያዩ መስመሮች፣ ለምሳሌ ሳላፊስቶች፣ ሽይቶች፣ ሱኒቶችና ውሃቢቶች የተከፋፈለ ስለሆነና፣ ይህም በህብረተሰብአችን ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል የአገራችን ጉዞ ወዴት እንደሚያመራ ከአሁኑ መናገር ያስቸግራል። ይህም ማለት ከቁጥጥር ውጭ የወጣ የሃይማኖት መስፋፋት ህብረተሰቦችና አገሮች ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች እንዳያደርጉ ያግዷቸዋል። ታሪክን ለመስራት እንዳይችሉ ይሆናሉ። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆኑ መንገዱ ሁሉ ይጨልምባቸዋል።

       አንዳንድ የሳይኮሎጂ ምሁራን እንደሚሉት ሃይማኖት በጣም ብልህ ሰዎች የፈጠሩት ጉዳይ እንደሆነ ነው። ይሁንና ግን ሊታለፍ የማይችልና ማንኛውንም ህብረተሰብ ሊያሰትሳስርና፣ ማድረግ የሚፈልገውን እንዳያደርግ ሊገድብ የሚችል እንደሆነ ያሰተምራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ባለፉት ሺህ ዐመታት መጽሀፍ ቅዱስም ሆነ ቁራን በተለያዩ ምሁራን ልክ እንደፍልስፍናም የተለያዩ ትርጉም እየተሰጣቸው ሲያወዛግቡ ይታያሉ። በዚህም የተነሳ ሃይማኖትን በሳይንስ መነጽር መርምሮ ይኸኛው መንገድ ነው ትክክል ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ምክንያቱም ሃይምኖት የዕምነት ጉዳይ እንደመሆኑ መጠንና የሚታፊዚክስ ጉዳይ ስለሆነ ከአቅማችን በላይ የሆነውን ነገር ማረጋገጥ ስለማይቻል ነው። አንዳንድ ሎጂካዊ ጥያቄ ማቅረብና መልስ መስጠት ቢቻልም እንኳ በሃይምኖት ላይ ብዙ ጥያቄ እንዲነሳባቸው የማይፈልጉ አሉ። ስለዚህም ሃይማኖትን እንደህብረተሰብ ወይም እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ እየተነተን በዲያሌክቲካዊና በምርምር መነፅር ማረጋገጥ አይቻልም። በሌላ ወገን ግን የማሰብ ኃይል ስላለን ተቻችሎ የመኖርና፣ የዚኽኛውን ወይም የዚያኛውን ሃይማኖት ፈለግ አክብሮ መቀበል የግዴታ ነው። በሃይማኖቶች መሀከል መከባበር መኖር አለበት። አንደኛው ከሌላ እበልጣለህ ብሎ የሚነሳ ከሆነ በቀላሉ ልንፈታው የማንችለው አዙሪት ውስጥ ነው የምንወድቀው።

       የሃይማኖትን ነገር ስናነሳ መረሳት የሌለበት ጉዳይ፣የትኛውም ሃይማኖት ይሁን ለማንኛውም ህብረተሰብ አስፈላጊ የሆነውን ያህል፣ ማንኛውም ሃይማኖት በራሱ ሰፊና እየተወሳሰበ የመጣውን የህብረተሰብ ችግር ሊፈታ የሚችል አይደለም። ለመኖር ስንል መብላትና መስራት አለብን። ስንሰራ ብቻ ገንዘብ ማግኘትና፣ ለህይወታችን የሚሆኑ ነገሮችን መግዛትና መኖር እንችላለን። ካልበላን እንራባለን። ከተራብን ደግሞ ሁኔታው እየዘገየ ከሄደ ሴሎቻችን በምግብ እጥረትና በውሃ ችግር ይሞታሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ በተወሳሰበ ዓለም ውስጥ ሃይማኖትን የሳይንስ መተኪያ ልናደርገው አንችልም። በሳይንስ አማካይነት ብቻ ነው ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የምንችለው። ቴክኖሎጂዎችን ስንፈጥር ብቻ ነው በቁጥር እየጨመረ የሚሄደውን ህዝብ መመገብ የምንችለው። በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው የህክምና መሳሪያዎችንና መድሃኒቶችን መስራት የምንችለው። በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ለመገናኛና ለመመላለሻ የሚሆኑ፣ መኪናዎችን፣ ባቡሮችንና አውሮፕላኖችን መስራት የምንችለው። በሌላ አነጋገር የሳይስን ትርጉም ቦታ ካልሰጠነው፣ ፖለቲካንና ሃይማኖትን ብቻ የምናስቀድም ከሆነ እግዜአብሄር የሚለውን ቃል ጣስን ማለት ነው። በሳይንስ አማካይነት ከየት እስከየት መሄድ አለብን፣ ምን ምን ነገሮች ብቻ መሰራት አለብን የሚለውን በቀላሉ የሚመለስ ጉዳይ አይደለም። የፍልስፍናና የኤቲክስ ጉዳይ ነው። አቶም ቦንብንም ሆነ የኬሜካልና የባዮሎጂን የማጥፊያ መሳሪያዎች  መስራትና አለመስራቱ ጉዳይ የስነ-ምግባር ጥያቄ ነው። ይሁንና ግን ለብዙ ነገሮች ገደብ ማድረግ ይቻላል። ይህ ደግሞ የአንድ አገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው የዓለም ማህበረ-ሰብ መወያየት ያለበት ጉዳይ ነው። በዚህም ብንል በዚያም ለመኖር ከፈለግን ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ልናመልጥ አንችልንም።

        ወደ  ህብረተሰብ ጉዳይም ስንመጣ አንዳንድ አገሮች የስራ ክፍፍልን፣ የዕደ-ጥበብን ማስፋፋት ጉዳይ፣ ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችን የመገንባት ጉዳይ፣ ከተማዎችን በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች ማገናኘትና፣ የሃሳብና የንግድ ልውውጥ ማድረግ፣ ወዘተ… እየሳቱት የመጡ ይመስላሉ። አብዛኛውን ጊዜ እንደኛ ያሉ ህብረተሰቦችና ብዙ የአፍሪካ አገሮች ህብረተሰብአዊ ውዝግብ ውስጥ የሚገቡት ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅና ለመመለስ ስለማይችሉ ነው። ስለሆነም ቢያንስ ከመቶ ዐመት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው የኃይል አሰላለፍና፣ በተለይም ባለፉት ሰላሳ ዐመታት በግሎባላይዜሽን ስም ብዙ ውንብድናና ማሳሳት ስለሚካሄድና፣ የዚኽኛው ወይም የዚያኛው ኃያል መንግስት አቀብቃቢዎች እየተፈጠሩና ስልጣን እየያዙ ብዙ ህብረተሰቦችን ወደ ጥፋት እንዲያመሩ እያደረጉ ነው። ባለፉት ሃያ ስምንት ዐመታት በአገራችን ምድር አንዱ ምህር እንዳለው፣ ብዞ አስመሳይ(ሶይዶ) የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው በመፈጠርና በጮሌነት ወደ ስልጣን አካባቢ በመጠጋትም ሆነ በንግድ መስክ ውስጥ በመሳተፍ የህብረተሰብአችንን ችግር ከመፍታት ይልቅ ህዝባችን በድህነት እንዲማቅቅ አድረገዋል። ይህ ዐይነቱ ከፍተኛ ወንጀል ያልታያቸው ተባባሪ በመሆን ችግሩ ከምን እንደመነጨ ግልጽ ውይይት እንዳይደረግ አግደዋል። ዛሬ በአገራችን ምድር አፍጦ አግጦ የሚታየው ድህነት፣ የቆሻሻ ቦታዎች ማደሪያ መብዛት፣ የከተማዎች መፈራርስና የሰው የተዘበራረቀ ኑሮ መስፋፋት፣ በከተማዎች ውስጥ ቀማተኛና ማጅራት መቺ እንደገና መስፋፋትና ህፃናትንና ሴቶችን መድፈርና እስከ መግደልም መድረስ፣ ባልቴትና ሽማግሌዎች በፍርሃት ዓለም እንዲዋጡ ማድረግና፣ አንድ ህብረተሰብ በዘለዓለማዊ ፍርሃትና የጦርነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድርግ፣ ከሰማይ ዱብ ያሉ ነገሮች አይደሉም። ካለማውቅና ካለማሰብ የተሰሩና የተፈጠሩ ነገሮች ናቸው። የህብረተሰብን አገነባብ ህግ ካለማወቅም ሆነ ለማወቅ ካለመፈለግ የተነሳና፣ ዛሬ በልቼ፣ ዛሬ ተደስቼና ጨፍሬ ልሙት ከሚለው እጅግ አደገኛ ስሌት የመነጨ መጥፎ አካሄድ ነው። ከዚህም ባሻገር ካለፊት ኡለት ዐመታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ የዲሞግራፊ ለውጥ ማካሄድ አለብን ተብሎ ከገጠር ውስጥ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማስፈር ከፍተኛ አለመረጋጋትንና አለመተማመንን ፈጥሯል። ኗሪውን ህዝብ የሚገፈትሩና እንዲያም ሲል የሚያስፈራሩና የሚደበድቡ በየቦታው ተሰማርተዋል። እነዚህ መጤ ኃይሎች ከመንግስት መኪና ጋር ወይም ከአንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች ጋር በመቆላለፍ ወደ ማጅራት መችነት፥ ዘራፊነትና ገዳይነት ተሰማርተዋል። ለዚሁ ዋናው ምክንያት ስልጣንን የጨበጠው አገዛዝና የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪዎች የፖለቲካን ትርጉም በቅጡ አለመረዳታቸውና በዚህ ዐይነት ፖለቲካቸው እንደ ኢትዮጵያ የመሰለን አገር ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር እንችላለን ብለው በመገመታቸው ነው።፡

         በቡሃ ላቆ ጆሮ ደግፍ ተጨምሮበት እንዲሉ፣ ይህ ሁሉ ትርምስ እያለ ነው አሁን ደግሞ በተለይም የጎሳ ጥያቄ ልዩ አጀንዳ ሆኖ የመጣው። ይህንን አስቸጋሪና የፖለቲካ ስርዓቱ የወለደውን አደገኛ ሁኔታ ለመፍታት አገዛዙ ከጎሳው ባሻገር መመልከት አለበጥ። ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተወለደ ግለሰብ እራሱን እንደ አንድ ዜጋና ሰው መቁጠር አለበት፤ እንዲሁም በአርቆ አሳቢነት የሚመራ መሆን አለበት። በአገራችን ምድር በጎሳና በሃይማኖት ስም ፖለቲካ መካሄድ የለባቸውም። ፖለቲካ እያንዳንዱን ግለሰብና ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚመለከት እንደመሆኑ መጠን ችግሮቹ ሁሉ ሊፈቱ የሚችሉት በሳይንስና በፍትሃዊነት መንገድ ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ያሉትና አፍጠው አግጠው የሚታዩት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም። በአገራችን ምድር ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት ከፈለግን ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ትዕዛዝ መላቀቅ አለብን። በቀላልና በግልጽ ማሰብ መቻል አለብን። ሎጂክንና ሳይንስን ማስቀደም አለብን። በቀላሉ ልንፈታ የምንችላቸውን ችግሮች የባሰውኑ ውስብስብ አናድርጋቸው። በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር የሚታየውን ችግር ልንፈታ የምንችለው በአንድ በኩል የአገራችንን የተወሳሰበ ሁኔታ ስንረዳ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ የሚሸረብብንን ተንኮል በግልጽ ስንወያይ ብቻ ነው። ስለዚህም ትንሽም ቢሆን እንኳ ደፋርና ሀቀኛ ለመሆን መሞከር አለብን። ይህም ማለት፣ በተለያዩ የህብረተሰብ ጥያቄዎች መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት በሎጂክ መነጽር በመመልከት ውይይት ለማድረግና መፍትሄ ለመስጠት መሞክር አለብን። ቶሎ ብለን ፍርድ በመስጠት ወደ ውንጀላና ፍጥጫ አለመግባት። ከዚህም ባሻገር የራሳችን ችግር ፈቺዎች ራሳችን መሆናችንን መገንዘብ አለብን። ማንኛውም ኃይል ሆነ መንግስት የኛን ችግር ሊፈታልን አይችልም። በሌላ ወገን ግን ዛሬ ሃይማኖትንም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ጥያቄዎችን  አሳቦ የሚካሄደው ውይይት ጥልቀት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በከፍተኛ የምሁራዊ መነጽር እየታየ ለውይይት መቅረብ አለበት። እንዲያው ለሺህ ዐመታት ያህል ተቻችለን ኖረናል በሚል ብቻ የሚፈታ አይደለም። በተረፈ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤንነትና የትብብር እንዲሁም የዕውቀት ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኝላችኋለሁ። መልካም ግንዛቤ!

                                                                             fekadubekele@gmx.de