[gtranslate]

ዋናው ጥያቄ ስልጣንን መጨበጥ አይደለም! አስቸጋሪው ነገር ጠንካራ

 የሆነና ፍትሃዊነት የሰፈነበት አገር እንዴት መገንባት ይቻላል የሚለው ነው!!

                                                               ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

                                                                 መጋቢት 31፣  2020

                               „ We are just leaving barbarism and are still entirely at the beginning. The French,

                      however have already gone a piece of the way and have a century`s lead in every  respect.”   Friedrich the Great II to Wilhelm of Prussia

መግቢያ

ዶ/ር አቢይና የሚወክሉት ድርጅታቸው ኦዴፓ ስልጣንን ከጨበጡ ይኸው ሁለት ዓመት ሊጠጋቸው ነው። በተለይም ዶ/ር አቢይ ስልጣን ሲጨብጡ ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት ከእንግዲህ ወዲያ ውድ አገራችን ስላም የሚሰፍንባት፣ ዲሞክራሲ የሚያብባትና ቀስ በቀስም ወደ ብልጽግና የማምራት ዕድል ልታገኝ ትችላለች የሚል ዕምነት ነበረን። በተለይም ሁሉም እንደተማረውና እንደተሰጥዎ የበኩሉን አስተዋፅዖ ካዳረገ ቀስ በቀስ፣ ይሁንና ደግሞ በእርግጠኝነት ሰላምና ፍትሃዊነት የሰፈነባት አገር ማየት እንችላለን የሚል ግምት ነበረን። ከእንግዲህም ወዲያ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ ቡድን እወክልሃለሁ የሚለውን ብሄረሰብ ተገን በማድረግና በማሳበብ፣ ወይም ደግሞ ከዚህ በፊት ስንበደልና ስንናቅ ነበርን፣ አሁን ደግሞ ተራው የእኛ ነው በማለት የሚንደላቀቅበትና ወደ ጦርነት የሚያመራበት ዘመን ያከተመ መስሎን ነበር። ከእንግዲህ ወዲያም የከፋፍለህ ግዛውና የሽወዳው ዘመን አልቆ ፖለቲካ የሚባለው ትልቅና ከፍተኛ ትርጉም ያለው ፅንሰ-ሃሳብ በእውነትም ፖለቲካ መሆኑ የሚገለጽበትና፣ ስልጣንንም የጨበጠው ኃይል ህገ-መንግስቱን የሚያከብርና ወይም ደግሞ ከዚህ በፊት ሲሰራበት የነበረው ህገ-መንግስት ጉድለት ካለው በአዲስና ጠቅላላውን ህዝብ በሚመለከት ረገድና ከዘላቂ ሰላምና ከሁለ-ገብ ዕድገት አንፃር በመታየት እንደገና በመጻፍ የህዝባችን አለኝታ በመሆን ሰላምና ዕድገት የሚታይባትና የሚያብቡባት ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን ብለን ነበር። ይህንን ዐይነቱን ህልማችንና ዕምነታችንን ሳናይ ሁለት ዐመት ሊጠጋን ነው።

ከዛሬው ሁኔታ ስንነሳና ወደ ኋላ ተመልሰን ከሃያ ሁለት ወራት በፊት የነበረንን የመንፈስ ደስታና መረጋጋት ስንመረምር አገራችን እንደዚህ ዐይነቱ ውስብስና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትወድቃለች ብለን የቅንጣትም ያህል የቆጠርን ያለን አይመስለኝም። በታሪክ ውስጥ በተለይም በህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የተጠበቀው ነገር ሳይሆን ሁልጊዜ ያልተጠበቀው ነገር ነው የሚከሰተው። በእርግጥም የታሪክን ሂደት ሙሉ በሙሉ በመተንበይ ከተወሰነ ዐመታት በኋላ እንደዚህ ዐይነት ነገር ሊፈጠር ይችላል ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። በተለይም በዛሬው የተንዛዛና የሚያሳስት የኢንፎርሜሽን ዘመንና፣ ሁሉም እንደፈለገው በሚፈነጭበትና የነገሮችን ሂደት ሳይገናዝብና የአንድንም ህብረተሰብ ችግር በዚህ መልክ መፍታት እችላለሁ ብሎ መመሪያ ወይም ፕሮግራም ሳያወጣ ዝም ብሎ የዚህ ብሄረሰብ ተወካይ ነኝ ብሎ በሚፈነጭበት ዓለም ውስጥ የታሪክን ሂደት መልክ ለማሲያዝ በጣም አስቸጋሪ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የጂኦ-ፖለቲካ ጥቅም አለኝ የሚሉና እንደኛ ያለውን በደንብ ያልተደራጀ ህዝብና ደካማ የመንግስት ተቁማትና ለጥቅም የተገዛ ኤሊት ተገን በማድረግ አንድ አገር ፋታ እንዳያገኝ የተንኮል ስራ በሚሸርቡበት ዓለም የአንድን አገር ሂደትና የመጨረሻ ውጤት መተንበይ በጣም አስቸጋሪ ነው።

ያም ሆነ ይህ በተለይም ባለፉት ሃያ ሁለት ወራት ያልጠበቅነው ነገር በአገራችን ውስጥ መከሰቱና ዛሬ ህዝባችን በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር መገደዱ ሁላችንንም ሀዘን ውስጥ ከትቶናል። ከዚህ ስንነሳ አብዛኛዎቻችን መጠየቅ የተገደድነው የዶ/ር አቢይ ወይም የቲም ለማ የሚባለው ቡድን ስልጣንን መጨበጥ ለህዝባችን „እርግማን ወይስ ቡራኬ„ ነው የሚል ነው። በተለይም ጊዜው የእኛ ነው ብለው ብቅ ያሉና የመንግስትን መኪና በቀላሉ መጨበጥ የሚችሉ የመሰላቸው አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች በውጭ ኃይሎች እየታገዙ የሚያደርጉት የጥላቻ ቅስቀሳና ያልተደረገንና በእርግጥም በሳይንሳዊ ጥናት ያለተረጋገጠን ወሬ ሲያናፍሱ ስንሰማ ሁላችንንም የአገራችንና የህዝባችን ሁኔታ ያሳስበናል። በተለይም ደግሞ መንግስት የሚባለው ፍጡር በእንደዚህ ዐይነቱ የጥፋት አጀንዳ ባላቸው ግለሰቦች ዘንድና በቡድንም ተደራጅተው ትርምስ መፍጠርና እርስ በእርስ መተማመን እንዳይኖር በሚያደርጉት ዘንድ ልፍስፍነትን ሲያሳይ ስንመለከት የአገዛዙንም ዋና ተልዕኮ እንድንመረምር እንገደዳለን።

የዚህ ጽሁፍ ዋናው መልዕክት በድርጊቶቹ ላይ ሳይሆን የሚያተኩረው እንደዚህ ዐይነቱ ችግር ለምንድነው የሚከሰተው?  የሚለውን ጥያቄ በማንሳት በርዕይ፣ በፖለቲካ፣ በስርዓትና በጠቅላላው በኢኮኖሚ አገነባብና ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ ያለውን አስቸጋሪ የግንዛቢ እጦት ግልጽ ለማድረግ ነው። በተለይም እንደኛ በመሰለው ባልረጋና በእያንዳንዱ የአገርና የህብረተሰብ ጥያቄ ላይ ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ጥናትና ክርክር በማይደረግበት አገር ውስጥ ዝም ብሎ በጭፍን በፖለቲካ ስም የሚደረገው መሯሯጥ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠፋፋት እንደሚያመራን ለመጠቆም ነው። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የአገዛዝ መለወጥ ሳይሆን አስቸጋሪው ነገር፣ እንዴት አድርጎ ነው ጠንካራና የተረጋጋ አገር መገንባት የሚቻለው?  በሚለው ላይ ማጥናትና መወያየት የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄና መልስም የሚያሻው ነው ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በመነሳት መሰረታዊ ናቸው የምላቸውን ፅንሰ-ሃስቦች በቅደም ተከተል ግልጽ ለማድረግ እሞክራለሁ።

ለምን ዐይነት ርዕይ ነው የምንታገለው?

በመሰረቱ አሉታዊ የሆነ ወይም የጨለመ ርዕይ የለም። ርዕይ ሁልግዜ ተስፋ ሰጪና ከቆንጆ ነገር ጋር የተያያዘ ነው። ይሁንና ግን አንዳንዶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዚኸኛው ወይም በዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም በመጠመድ ለቆንጆ ነገር እየታገሉ አየመሰላቸው የአንድን ህዝብ ፍላጎት ወደማጨለም ያመራሉ። ለምሳሌ ሽብርተኛ ተብለው የሚፈረጅባቸው ራሳቸው በሃይማኖት ሽፋን ስር በመሰለፍና ለቆንጆ ነገር እየታገሉ እየመሰላቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን በማሳሳት ጨለማዊ ኑሮ እንዲኖር ያደርጉታል። አንድን ህዝብ ጭፍን የሃይማኖት ሰለባ በማድረግ በማሰብ ኃይሉ ሊሰራ የሚችለውን ነገር እንዳይሰራና ኑሮውን አሻሽሎ ሰላማዊ ኑሮ እንዳይኖር ያግዱታል። ይህ ዐይነቱ ችግር አብዛኛውን ጊዜ የሚመነጨው ፈልሳፋዎች እንደሚሉት ሰዎች አርቆ የማሰብ ኃይላቸውን መጠቀም የማይችሉ ከሆነ ነው። በተጨማሪም ጭንቅላታቸው በትክክልኛና መንፈስን በሚያድስና በሁሉም አቅጣጫ እንዲያሰብ በሚያደርግ ዕውቀት ካልታነፀ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች በቀላሉ የርዕዮተ-ዓለም ወይም የጠባብ ጎሰኝነት አስተሳሰብ ሰለባ በመሆን አንድን አገር ያተራምሳሉ። በተለይም የውጭ ኃይል መሳሪያ በመሆን አንደኛውን ጎሳ ከሌላኛው ጋር በማጣላት ይህንን የአገዛዝ ፈሊጥ በማድረግ ህብረተሰቡ ጨልሞበት እንዲኖር ያደርጋሉ። በተለይም የተወለዱበት አካባቢና ቤተሰብ፣ ያደጉበትና የቀሰሙት ትምህርት  ባህላዊ ዕምርታን ካላገኘ ወይም በአካባቢው መንፈስን የሚያድስ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ከሌለ ይህ ዐይነቱ ውስን ማህበረሰብ በታዳጊውና በተለይም ስልጣንን ለመጨበጥ በሚፈልገው ግልሰብም ሆነ ቡድን ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ማንም ሰው ከመጥፎ አስተሳሰብ ጋር አወለድም። ይሁንና ግን አንድ ሰው ሲወለድ የሚወረወርበት ህብረተሰብአዊ አወቃቀር፣ ባህላዊ ክንዋኔና የዕድገት ደረጃ ቀስ በቀስ አስተሳሰቡን እየቀረጹት፣ አርቆ-አሳቢ ወይንም ደግሞ አርቆ-የማያስብ በመሆን አይ ለቆንጆ ነገር ይታገላል፤ ካሊያም ደግሞ አስተሳሰቡ ስንኩል በመሆን ወደ በጥባጭነትና ወደተንኮል ተብታቢነት በማምራት የሰው ልጅ ኑሮ እንዲጨልም ያደርጋል። ለምሳሌ የአንዳንድ ፈላስፎችን፣ ገጣሚዎችንና የድራማ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ስናነብ እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያውኑ ከጥሩ ሁኔታ ጋር ስለተጋጩና ቤተሰቦቻቸውም እየተከታተሏቸው ስላስተምሯቸው በማሰብ ኃይላቸው ጥሩ ነገር ሰርተውና፣ ለጠቅላላው የሰው ልጅ የሚሆን የስልጣኔ መመሪያ ጥለው ለማለፍ በቅተዋል። በጣም ጥቂት ካልሆኑት በስተቀር አብዛኛዎቹ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ከአሪስቶክራሲው መደብ ወይም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከነበሩት ቤተሰቦች የተወለዱ ናቸው። ይሁንና ግን የመጡበትን መደብ አስተሳሰብ አሽቀንጥረው በመጣል ለጠቅላላው የሰው ልጅ የሚሆን የስልጣኔ መሰረት ጥለዋል። አብዛኛዎቹም በተግባር ተተርጉመዋል። ዕውቀታቸውም ዘለዓለማዊነት ያለው ነው። አብዛኛዎች ዕውቀቶች ከሁለት ሺህ ዓመትና ከስድስት መቶ ዓመታት በፊትም ቢፃፉም ዛሬም ቢሆን ትርጉምነታቸውን ያጡ አይደለም።

ከዚህ ስንነሳ የእኛ ለጥሩ ነገር መታገል ወይም ለአንዳች ርዕይ እዚህና እዚያ መሯሯጥ በመሰረቱ ከላይ ከጠቀስኩት ሁኔታ ውጭ ሊሆን አይችልም። አስተሳሰባችን የህብረተሰባችንና የዚህ ዓለም ውዝንብር ርዕዮተ-ዓለም ውጤት በመሆኑ፣  ርዕያችንም በዚህ የሚወሰን ነው። በግልጽ ለመወያየት፣ ሃሳብን ሳንገድብ ለመከራከርና ወደ አንዳች ፍሬያማ ነገር ለመምጣትና፣ ህዝባችን የሚመኘውን የበለጸገና ሰላማዊ ኑሮ ለማስፈን ከመጀመሪያውኑ የተቀረጽንበት ርዕዮተ-ዓለምና አስተዳደጋችን ይወስኑታል። እንደሚታወቀው ትናትም ሆነ ዛሬ፣ ምናልባትም ወደፊት በየአገሮች የሚኖሩ ህዝቦች ዕጣና ርዕያቸውን ዕውን ለማድረግ ተማርኩ ወይንም ኤሊት ነኝ በሚለው የሚወሰን ነው። የዓለምን ታሪክ ላገላበጠ፣ በዚህም በዚያም ብሎ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያለ፣ አይ ጥሩ አገር በመገንባት ይታወቃል፤ ካሊያም ደግሞ በጨለማ አስተሳሰብ በመጠመድ የአንድ ህዝብ ዕድል የጠመመ እንዲሆን ያደርጋል ። በታሪክ ውስጥ በማንኛውም አገር አንድ ህዝብ ይህን ነገር ነው የምፈልገው ብሎ በመነሳት የራሱን ምኞት ተግባራዊ ለማድረግ የቻለበት ጊዜ አልነበረም። በሌላ ወገን ግን የሰው ልጅ እንደማህበረሰብ ከመደራጀቱና የስራ-ክፍፍል ወደማዳበር ሲያመራ በራሱ የማሰብ ኃይል በፈቃድ በመተባበር በተናጠልም ሆነ በጋርዮሽ አንዳንድ ነገሮችን እንደሰራና ሰላማዊ ኑሮም ይኖር እንደነበር የተረጋገጠ ነው። ይሁንና ግን የአንድ ህብረተሰብ አወቃቀር እየተወሳሰበ ሲመጣና፣ የስራ-ክፍፍል ሲዳብር መንግስት የሚባለው ነገር በመፈጠር ስልጣንና ሀብትን በመቆጣጠር የአንድን ህዝብ ዕድል ወሳኝ ወደመሆን አመራ። በተወሳሰበ መልኩም ቢሆን ዛሬም ያለው ሁኔታ ይህ ነው። በሌላ አነጋገር የሀብት ፈጠራና የሀብት ክፍፍል ምንጭ ሊሆንና፣ በአንድ አገር ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት መኖርና አለመኖር ወሳኝ ሚናን የሚጫወተው በስልጣን ላይ ያለው ኃይልና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኤሊት ነኝ የሚለው በሚመራበት ርዕይና ንቃተ-ህሊና የሚወሰን ነው።

ስለሆነም የረዥሙን የተወሳሰበ የህብረተሰብችንን ታሪክ ሁኔታ ወደ ጎን ትተን፣ ከአርባ ዐመታት ወዲህ የህዝባችን ዕጣና የህብረተሰብአችን ዕድገት ሊወሰን የቻለው፣ በአንድ በኩል በወታደሩ አገዛዝና በወያኔ መንግስት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ለብሄረ-ሰባችን ነፃነት እንታገላለን በሚሉትና በጠቅላላው በኤሊቱ ነው። በተለይም ባለፉት 40 ዐመታት ብሄረ-ሰቤን ነፃ አወጣለሁ ብለው ከሚታገሉ „ድርጅቶች“ ባሻገር የኢትዮጵያ ነገር ያገባኛል የሚሉና፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ካለኔ ድርጅት በስተቀር ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ርዕይ ያለውና ዕድሉንም ሊወስን የሚችል ሌላ ድርጅት የለም እያሉ አምረው የታገሉና የሚታገሉ፣ እነዚህ ሁሉ በህዝባችን የትላንትናውና፣ የዛሬው፣ እንዲሁም የወደፊቱ ጥሩ ወይም መጥፎ አኗኗር  መመስረት ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፤ ይጫወታሉም። አንደሚወራው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ወደሰማንያ የሚጠጉ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል። የአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ፍልስፍናና ርዕይ፣ አንዲሁም አደረጃጀትና አገርን የመምራት ብቃት በሚገባ የሚታወቅ ነገር አይደለም። ከዚህ ስንነሳ ለብሄረ-ሰቤም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነትና ደህንነት እታገላለሁ፣ የተሻለ የትግል ልምድም አለኝ የሚሉት ሁሉ፣ ምን ዐይነት ፍልስፍና እንዳላቸውና፣ ስልጣን ቢይዙ እንኳ በምን ዐይነት ፖሊሲ እየተመሩ የተተራመሰውንና የተመሰቃቀለውን የአገራችንን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የህብረተሰብ ችግሮችና፣ እንዲሁም የባህል ቀውስ እንደሚፈቱና ስርዓት ባለው መልክ ማስተካከል እንደሚችሉ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም። በአጠቃላይ ሲታይ የአንድ ህዝብ ርዕይ በተግባር የሚመነዘር መሆን አለበት። የሚታይ መሆን አለበት። የሚዳሰስ መሆን አለበት። የሚበላና የሚቀመስ መሆን አለበት። በአንድ ህዝብ አኗኗር ላይ ትርጉም የሚኖረውና፣ የአንድን ህዝብ የፈጠራ ችሎታ የሚያዳብር መሆን አለበት። ርዕይ ሲባል አንድን ህዝብ ታሪክ የሚያሰራው መሆን አለበት። በአንድ ወቅት የሚከሰትና ቡግ ብሎ እንደሚጠፋ እሳት ሳይሆን፣ ተከታታይነት የሚኖረውና፣ ከአንድ ትውልድ ወደሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ መሆን አለበት። ርዕይ ሲባል በጥሩ መሰረት ላይ የሚገነባና በቀላሉ የማይገረሰስ መሆን አለበት። በዚኸኛው ወይም በዚያኛው አዲስ ኃይል ሊናወጽ የማይችል፣ ወይም ደግሞ የውጭ ኃይል እየገባ እንደፈለገው የሚፈተፈትበትና፣ ወጣቱን የሚያሳስትበት ሁኔታ መሆን የለበትም። እንደሚታወቀው ርዕይ እንደ ዓላማ የሚታይ ቢሆንም፣ እዚያው በዚያው ክንውናዊ(Process)ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ነገር ቢሆን በደረጃዎችና በዕድገት የሚወሰን ስለሚሆን፣ ወደ አንዳች ርዕይ ለመድረስ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ድርጅት ወይም የብሄረ-ሰብ ነፃ አውጭ ነኝ የሚል ሁሉ ከመጀመሪያውኑ የሚመራበት ፍልስፍና ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በአንዳች ዐይነት ፍልስፍና የማይመራ፣ ዝም ብሎ ጠብመንጃ እያነሳ  ነፃ መውጣት አለብኝ የሚል ታጋይ ነኝ ባይ ሁሉ የመጨረሻ መጨረሻ ነፃ አወጣዋለሁ የሚለውን ህዝብ ወደ ጨለማ ኑሮ ውስጥ ይከተዋል። ይህንን ዐይነቱን ጭፍን ጉዞ ከአገራችን ታሪክ መማር እንችላለን። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ደግሞ፣ የሻብያ አገዛዝና፣ በአገራችን ምድር ደግሞ ከሃያ ስባት ዐመታት በላይ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያሉት ሰዎች ናቸው። የርዕያቸውንም ውጤት ህዝባችን ቀምሶታል፤ ዛሬም እንደመራራ ነገር እየተጎነጨው ይገኛል። የፖለቲካው መድረክ የማንም ፅንፈኛ ኃይሎች መጨፈሪያ በመሆን ህዝባችን ግራ ተጋብቶና ሁሉ ነገር ጨልሞበት ይገኛል።

ያም ሆነ ይህ በዛሬው ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀውና እንዲመለስለት የሚፈልገው ጥያቄ አለ።  ይኸውም አገሬን በታትንልኝ፣ በዚህም በዚያም ብለህ የውጭ ኃይል ባርያ አድርገኝ ሳይሆን፣ ተከብሬ የምኖርበትን አገር እንድመሰርት መንገዱን አሳየኝ ነው የሚለው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለው እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ወላይታ ወይም ኩሎ ኮንታ ነኝ እያለ የሚያናቁረውን፣ በመሰረቱ የውጭ ኃይል አቀንቃኝ የሆነውን ኃይል ሳይሆን፣ በዚህች አገር ሁላችንም እንደ አንድ ህዝብ በጋራ ተነስተን አገር እየገነባን የተረጋጋችና ተከባብረን የምንኖርባትን ኢትዮጵያ ለመመስረት ነው እያለ ነው ጩኸቱን የሚያሰተጋባው። ስለሆነም ጠብመንጃ አንስቶ ወይም ሳያነሳ እታገላለሁ የሚለው ኃይል በሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውን ርዕይ ዕውን ለማድረግ እስከዛሬ የሚመራበትን ፍልስፍና ወይም መመሪያ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን መመርመር ይኖርበታል።

ከዚህ ስንነሳ በየቦታው በአገርም ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ሃሳባቸውንና ርዕያቸውን ለማስረዳት የሚችሉ አይደሉም። አብዛኛዎቹ በምን ፍልስፍና ላይ በመመርኮዝ አዲስ አገር እንደሚገነቡ ሲያስተመሩን አይታይም። በየቦታው ሽርጉድ ሲባል አንድም ስበሰባ ላይ ምን ዐይነት ኢትዮጵያን ነው የምንፈልገው? በሚለው ላይ በጥናት መልክ ቀርቦ ውይይት ሲካሄድ አይታይም። በየአገሩ ከተማዎች የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባዎች ሲካሄድ አሰልቺ ንግግሮች ከመቅረባቸው በስተቀር፣ አንድም ሰው ቢሆን በመነሳት ኢትዮጵያችን፣ እንደህብረተሰብ እንደትገነባ ከተፈለገ፣ ተግባራዊ መሆን ያለበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይህ ዐይነቱ ነው ብሎ በጥናት መልክ በፓዎር ፖይንት አቀራረብ ሲቀርብ አይታይም። ጥያቄም የሚጠይቅም የለም። ብቻ ያለው የወደፊት ጉዞ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ ህዝብን ከማደናቆር በስተቀር ማንኛውም ቢሆን ለተወሳሰበው የአገራችን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የባህላዊ ችግሮች መፍትሄ ሲያቀርብ አይታይም። ስብሰባዎች በሙሉ የፊዩዳል ባህርይ ያላቸው የሚመስሉና ተንኮል የበዘባቸው እንጂ አንዳችም ምህራዊ ውይይትና ክርክር የሚካሄድባቸው አይደሉም። ተጋባዡም ሆነ አስተናጋጆች በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ማለትም በካፒታሊዝም የሊበራል ዲሞክራሲ ዘመን የሚኖሩ ሳይሆኑ በማዕከለኛው ዘመን የሚኖሩ ነው የሚመስሉት። ባጭሩ ንግግር የሚያቀርበውም ሆነ አስተዋዋቂ ሆነው ፖዲየሙ ላይ የሚቀመጡት በዘመናዊ አስተሳሰብ ወይም በአንዳች ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ የታነጹ አይደሉም። ጥያቄ መጠይቀና መከራከር የማይቻልበት፣ ወይም ለየት ያለ አማራጭ አስተሳሰብ ሲቀርብ ሁሉም በመደናገጥ ግራ የሚጋባ ነው።   ግራ የተጋባውም ምስኪን የውጭው ህዝብ ትሩ የሆኑ ምሁራዊ ትንታኔና መፍትሄውን ለመስማት ሳይሆን የሚፈልገው፣ ዝም ብሎ ለማድመጥና፣ የእነ አቶ አከሌን ንግግር ሰምቶ በሱ ረክቶ ለመሄድ ብቻ ነው። በእኔ ዕምነትና አመለካከት ይህ ዐይነቱ አካሄድ ታሪካዊ ወንጀል ከመፈጸም ውጭ ሊታይ አይችልም። ስለሆነም በእርግጥ ርዕይ አለን ብለን የምንታገል ከሆነና፣ በዚህ ወይም በዚያኛው ፍልስፍናና ፖሊሲ ነው የአገራችንን ችግር መቅረፍና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ማስወገድ የምንችለው ብለን የምናምን ከሆነ፣  ወደ ውጭ ወጥተን መከራከር፣ መወያየትና ግራ የተጋባውን ህዝባችንን ማስተማር አለብን። ህዝብን ግራ ከማጋባት ይልቅ በርዕይና በፍልስፍናና ላይ ያተኮረና፣ ደረጃ በደረጃ የህዝባችንን ችግር ሊፈታ ወደሚያስችል ፖሊሲና የአጻጻፍ ስልትና ክርክር ማትኮር አለብን። ከዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ በመነሳት ትክክል ናቸው ብዬ የማምንባቸውን ነጥቦችና የአፈታት ዘዴዎች በተናጠል አትታለሁ ። በመጀመሪያ ግን የስርዓት ጥያቄ ላይ ትንሽ እንቆይ።

 

የስርዓት ጥያቄ!

ስርዓት ማለት ምን ማለት ነው? ስርዓት የሚለውን በቀጥታ ወደ እንግሊዘኛው ሲይስተም ወደሚለው ብንተረጉመው የተሻለ ስዕል እናገኛለን። እንደሚታወቀው ማንኛውም ህይወት ያለው ነገርና እራሳቸው አትክልቶችም ሆነ ዛፎች ሁሉ በስርዓት የተደራጁ ናቸው። በተወሰነ የአውቃቀር ስልት የተዘጋጁ ናቸው። በራሳቸውም ውስጥ ራሳቸው የማደራጀትና የማደግ ውስጣዊ ኃይል አላቸው። ለምሳሌ ለጊዜው አንኳ ቢሆን በተፈጥሮ ውስጥ መናጋት ቢደርስ ተፈጥሮ በራሷ ውስጣዊ ኃይል በመረጋጋት ተናግቶ የነበረው ሁሉ በተፈጥሮ ራስን በራስ የማደራጀትና የማደግ ኃይል እንደገና ወደመስተካከል ያመራል። አትክልቶችም ሆነ ወደ ዛፍነት የሚለወጡት ችግኞች በውስጣቸው ራሳቸውን የማደራጀት ኃይል ውሃንና ሚኒራሎችን ከመሬት ውስጥ በመምጠጥና ለዕድገታቸው በመጠቀም፣ በጸሀይ ጨረር በመታገዝ ያብባሉ፤ ፍሬም ይሰጣሉ። የመጨረሻ መጨረሻ ፍሬ ካላቸው ፍሬያቸውን ለቅመን ለምግብ እንጠቅምባቸዋልን። ፍሬ የማይሰጡ ዛፎች ከሆኑ ደግሞ ለማገዶና ለቤት መስሪያ እንጠቅምባቸዋልን። ሰውነታችንም ቢሆን ራሱን የቻለ ሲይስተም ያለው ወይም በስርዓት የተደራጀ ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ ወይም በአንዳች በማይታወቅ ምክንያት ሰውነታችን አስፈላጊውን እንክብካቤ ሲያጣ የሰውነታችን ኦርጋኖች ወደ መናጋት ያመራሉ። የአጋጣሚን ነገር ወደጎን ትተን የእኛ በስርዓት መንቀሳቀና ማሰብ ወይም አዳዲስ ነገሮችን መፍጠርና ለህብረተሰባችን አስተዋፅዖ ማድረግ በእኛ በስነ-ስርዓት ማደግና ጭንቅላታችን በስነ-ስርዓት መቀረጽ የሚወሰን ነው። ንቃተ-ህሊናችንም ሆነ የኑሮአችንን ሁኔታ ሊወሰኑ የሚችሉት ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች ሲሆን፣ አስተዳደጋችን የተወሰነ እንከን ካለበት በቀላሉ ሊወገድ በማይችል አደጋ መጋለጥ አንችላለን። በሌላ ወገን ግን ከኛ ቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ በመጋለጥ የወደፊቱ አኗኗራችን ሁኔታና የህብረተሰብአችን ስርዓት የሚናጋበትና በቀላሉ ማስተካከል የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ያም ሆነ ይህ ለሰውነታችንም ሆነ ለጭንቅላታችን እንዲሁም ለማህበረሰብ ዕድገት የግዴታ በስርዓት መደራጀት፣ በስርዓት መንቀሳቀስ፣ በስርዓት ስራን መስራት፣ በስርዓት እያሰቡ መነጋገርና ወደ አንዳች ነገር ለመድረስ ስርዓት የሚባለው ነገር ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ስለሆነም ስርዓት የሚባለው ነገር ለአንድ ህበረተሰብ የጉዞ አቅጣጫ ነው ብሎ መናጋር ይቻላል። በሌላ ወገን ግን ህብረተሰብን ስርዓት ባለው መልክ ለማደራጀት ግብታዊነትም (Spontaneous) የሚጫወተው ሚና እንዳለ መዘንጋት የለብንም። አንድን ነገር በማቀድ ውስጥ ዕቅድና ግብታዊነት ጎን ለጎን ሊሄዱ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም።  ያም ሆነ ይህ አንድ ሰው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሲኖር በምን ዐይነት ስርዓት ውስጥ ነው የምኖረው? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። ማንኛውም ሰው ለመኖር ብቻ ስለማይኖር የኑሮን ትርጉም እንዲረዳ ከተፈለገ የሚኖርበትን ሁኔታ መጠየቅ አለበት። በስርዓት ሊያኖረው የማያስችለው ሁኔታ በስርዓት የተዋቀረ ስርዓት ካልሆነም ለምን የተዘበራረቀ ሁኔታ እንደተፈጠረና ህብረተሰብን እንደሚያዋክብ ራሱን መጠየቅ አለበት።

በአገራችን የተፈጠረው ችግር ስርዓት ሲባል ከርዕዮተ-ዓለም ጋር በመያያዝ ብዙ ሰዎችን ግራ ሲያጋባ ይታያል። በሌላ ወገን ደግሞ የግዴታ ሆኖ ህብረተሰብአችንን ስርዓት ባለው መልክ ለማደራጀት ከተፈለገ የግዴታ ርዕዮተ-ዓለም በሉት ፍልስፍና ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ግልጽ ለማድረግ፣ ህግን ወደጎን ትተን አንድ ህብረተሰብ ለመኖር ሲል የግዴታ በስራ-ክፍፍል መደራጀት አለበት። ሁሉም ተመሳሳይ ነገር ስለማያመርት ይህ ዐይነቱ የአደረጃጀትና የአመራረት ስልት የግዴታ  ወደልውውጥ ያመራል። በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የግዴታ በሳይንስ ላይ ወደተደራጀ የአሰራር ስልት ላይ ያመራናል ማለት አይደለም። ስራው ተደራራቢና አሰልቺ እንዳይሆን፣ ወይም ደግሞ አድካሚ እንዳይሆን ከተፈለገ በሳይንሳዊ ምርምር አማካይነት ወደተሻለ የአደረጃጀትና የአመራረት ስርዓት መዋቀር አለበት። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮችን መፍታትና ስርዓት ያለው ኑሮ መኖር የሚቻለው።

እስከዛሬ ድረስ በብዙዎቻችን ዘንድ ያለው አለመግባባት፣ አብዛኛዎቻችን ከንፁህ ርዕዮተ-ዓለም ጥላቻ በመነሳት ወይም ስርዓትን ከርዕዮተ-ዓለም ጋር በማያያዝ ወደማያስፈልግ ሽኩቻ ውስጥ እንገባለን። ብዙዎቻችን ለምርምር ጊዜ ስለሌለን በአንዳንድ ጮሌዎች በሚነፍስ ቅስቀሳ ወይም ጥላቻ በመጠመድ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ችግርን ለመፍጠር እናመራለን። ይህንን ግራ መጋባት መልክ ለማሲያዝ፣ ለመሆኑ ለምን ዐይነት ስርዓት ነው የምንታገለው? የሚለውን ጥያቂ ተቀራራቢ መልስ ለመስጠት ወይም አስታራቂ ነገር ለማቅረብ ወደ ውይይት እናምራ።

ስለማህበራዊ ስርዓት በምናወራበት ጊዜ በማውቅም ሆነ ባለማወቅ የአንድን ሀብረተሰብ ጉዞና ዕድል በገበያ ኢኮኖሚና በሶሻሊዝም መሀከል ነው የምንከልለው። የገበያ ኢኮኖሚ ችግራችንን የሚፈታልንና ሶሻሊዝም ደግም ጨለማዊ ስርዓትን እንደሚያጎናጽፈን አድርገን ነው የምንቆጥረው። በዚህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆን የሚታወቅ ነገር የለም። አንድ ህብረተሰብም ከገበያ ኢኮኖሚ ባሻገርና በብዙ ሺህ ድሮች የተሳሰረ ወይም መተሳሰር እንዳለበት ግልጽ የሆነልን አይመስልም። ይህ ዐይነቱ በደንብ ያልተጠና አስተሳሰብ በጭንቅላታችን ውስጥ ስለተቀረፀ አንድን ህብረተሰብ እንደ አንድ ወጥና፣ በሁለት አማራጭ መሀከል ብቻ እንደሚካሄድ ትግል አድርገን  በመቁጠር ሰፋ ያለና በጥናት ላይ የተመረኮዘ ውይይት እንዳይካሄድ ከመጀመሪያውኑ ኡእሃሳብ ዕገዳ እናደርጋለን። በሌላ ወገን ግን ጊዜ ወስዶ ለሚመራመርና ለሚጽፍ በታሪክ ውስጥ አንድ ወጥ ስርዓት የለም። ሌላው ቢቀር ሁሉም ነገር በገንዘብ በሚለካበትና በሚተመንበት የካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ ስርዓቱን እየተቀናቀኑ የሚኖሩ የአሰራር፣ የአመራረትና የአከፋፈል ሁኔታዎች አሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ዐይነት ኢፊሲያላዊ የገንዘብ መሽከርከርና የክፍያ ዘዴ ባለበት በካፒታሊስት የገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ እዚያው በዚያው ጎን ለጎን የሚንቀሳቀስ በሎካል ደረጃ የሚሽከረከር የገንዘብ ዐይነት አለ። በሌላ አነጋገር፣ ከዶላርና ከኦይሮ ውጭ ሌሎች የመገበያያ የገንዘብ ዐይነቶች አሉ ማለት ነው። ይህንን ዐይነቱን የልውውጥና ተቀባይነት ካለው ስርዓት ውጭ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ አትመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸውና በራሳቸው የሚተማመኑ ብቻ ናቸው። ይህም ማለት ምን ማለት ነው? አንድን ነገር በጥቁርና በነጭ መሀከል እየሳልን ይህንን ወይም ያኛውን ምረጥ እያልን የምንፋለም ከሆነ ሰፋ ያለና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እንዳይዳይዳብርና ባህልም እንዳይሆን ከመጀመሪያውኑ እናግዳለን ማለት ነው። በተጨባጭም ዕድገት እንዳይኖር እንቅፋት እንፈጥራለን።

ያም ሆነ ይህ አንድ ህብረተሰብ በኢኮኖሚዊ ስርዓት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ኢኮኖሚ የጠቅላላው ስርዓት አንድ አካልና መሰረት ነው። ይህም ማለት አንድ ህብረተሰብ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በርዕዮተዓለም፣ በኢኮኖሚና በልዩ ልዩ የአኗኗርና አመራረት ሁኔታዎች የሚገለጽ ነው። ከነዚህ በስርዓቱ ውስጥ ተጠቃለው ከሚታዩት ነገሮች ሁሉ ፖለቲካዊ አደረጃጀትና ንቃተ-ህሊና ወሳኝ ሚናን ሲጫወቱ፣ የሌሎች ንዑስ ክፍሎች በስርዓት መስራትና መንቀሳቀስ ሊወሰን የሚችለው በፖለቲካው ስርዓትና አደረጃጀት፣ እንዲሁም የንቃተ-ህሊና የዕድገት ደረጃ ነው። ፖለቲካዊ አወቃቀር ጤናማ በሆነበት ህብረተሰብና፣ በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና ፖሊሲዎች በሚነደፉበት ህብረተሰብ ውስጥ የሌሎች ንዑስ ክፍሎች ዕድገትና መዳበር መልክ ይይዛል። ሌሎች ንዑስ ክፍሎች ይፋፋሉ፤ ያድጋሉ።  ይህም ማለት በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ የሌሎች ንዑስ ክፍሎች ማደግና ሚናቸውን መጫወት የግዴታ በፖለቲካዊ ንቃተ-ህሊናና አደረጃጀት የሚወሰን ነው። በተጨማሪም ከፖለቲካዊ አደረጃጀት ባሻገር በየአንዳንዱ ንዑስ-ክፍል ውስጥ ያሉ ኃይሎች አንደኛው በሌላው ላይ ተፅዕኖ በማድረግ አንዱ የሌላውን ዕድገት ይወስናል። ይህም ማለት ማንኛውም ንዑስ-ክፍል በራሱ ብቻውን የሚጓዝ አይደለም ማለት ነው። በተለይም አሁን ባለንበት ነገሮችን ነጣጥሎ በሚታይበትና፣ የፖለቲካን ጉዳይ ለጥቂት ፖለቲከኛ ነን ባዮች በተጣለበትና በሚጣልበት ኢምፔሪሲስታዊና የሶፊስቶች ዓለም ውስጥ ፖለቲካና ፍልስፍና፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ህብረተሰብ እየተነጣጠሉ በመታየት ፖለቲካ ሳይንሳዊና ምሁራዊ ባህርዩን እያጣ በመምጣት ጥቂት ሰዎች እንደፈለጋቸው የሚፈነጩበት፣ ማህበረሰቦች ረጋ ብለውና ጥበባዊ በሆነ መልክ እንዳይደራጁና፣ አንድ ህዝብ ዘለዓለሙን እየተረበሸ እንዲኖር የማድረግ አዝማሚያ በጉልህ ይታያል። ብዙ አገሮች ወደ ጦርነት እያመሩ ነው። እጅግ አስቸጋሪ ዓለም ውስጥ ነን ያለነው ማለት ነው።

ይህ ዐይነቱ የአመለካከት ችግር የሚመነጨው ከምን የተነሳ ነው?  የብዙዎቻችን ችግር ለምሳሌ ዛሬ በዓለም አቀፍ የተሰፋፋውን የግሎባል ካፒታሊዝምና የገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ የታሪክ ሂደት ውጤት መሆኑን ለመቀበል አለመፈለግ ነው ። ከዚህም በመነሳት ይህ ስርዓት ድሮም የነበረና ወደፊትም የሚኖር፣ የመጨረሻው የሰው ልጅም ዕጣ ከሱ ጋር የተሳሰረ አድርጎ ከመወሰድ የተነሳ ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ የመነጨ ነው ብል እንደ ስድብ እንደማይቆጠርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለሆነም ሁሉም አገሮችና ህብረተሰቦች፣ ከታሪካቸውና ከባህላቸው፣ እንዲሁም ከልምዳቸውና ከህብረተሰብአቸው ባሻገር መቀበል ያለባቸው ስርዓት ነው። ይህ ዐይነቱ አጉል ውስንና አደገኛ አስተሳሰብ ህብረተሰብአችን ከሚፈልገውና ከሚጠብቀው ስርዓትና ከተጨባጩ የህብረተሰብ ሁኔታ ጋር ሊጣጣም የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ይህ ዐይነቱ አደገኛ አመለካከት ጥቂት ኢሊት ነን ባዮች ሳያወጡ ሳያወርዱ በህብረተሰብአችን ላይ የሚጭኑት ስርዓት ስለሆነና ስለሚሆን ህብረተሰብአችን የሚፈልገውን ነገር በፍጹም ሊያገኝ አይችልም።

ለምሳሌ የካፒታሊዝምን ስርዓት ስንመለከት ቀድሞውኑ ታቅዶና ተፈልጎ የተዋቀረ ስርዓት አይደለም። በታሪክ ሂደት ውስጥ የተፈጠረና በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሊዳብርና ሊስፋፋ የቻለ ነው። ስለካፒታሊዝም ስርዓት በምናወራበት ጊዜ ስርዓቱ እንደማህበራዊና እንደ ኢኮኖሚያዊ ቅንጅትና ክንዋኔ የዛሬውን መልክ ከመያዙ በፊት የምዕራብ አውሮፓ ህዝብ በአጋጣሚ ባገኘው ዕውቀት ሬናሳንስ የሚባለውን የጭንቅላትና የመንፈስ ተሃድሶ በማድረግና በአዲስ ዕውቀት በመመራት ሰዎች የማሰብ ኃይላቸውን ተጠቅመው የታሪክ ባላቤት እንዲሆኑ መንገዱ ይቀደዳል። ይህም ማለት የአውሮፓው ካፒታሊዝም ካለሪናሳንስ ወይም ካለመንፈስ ተሃድሶ ውጭ በፍጹም ሊታስብ የሚችል አይደለም። ይህ አዲስ የተፈጠረው ሁኔታ ለከተማዎች ዕድገት፣ ለዕደ-ጥበብ ማበብና ለንግድ መስፋፋት መንገዱን ይጠርጋል። በተለይም በሩቅ ንግድ አማካይነት የገንዘብ ሀብት ማከማቸት የቻለው ነጋዴ የሞናርኪዎችን ጦርነት ፋይናንስ የሚያደርግና፣ በተለይም ደግሞ የዕደ-ጥበብ ሙያን ወይም የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ቀስ በቀስ በቁጥጥሩ ስር በማድረግና አዳዲስ ምርቶች እንዲመረቱ ትዕዛዝ በመስጠትና ለገበያ በማቅረብ(Putting-Out system) አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም ባህል እንዲዳብር አደረገ።  ይህ በራሱ ደግሞ አዲስ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብርና በጊዜው የነበረውን ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ጋር እንዲጋጭ ያደርገዋል። በ14ኛውና በ15ኛው ክፍለ-ዘመን የተጀመረው የድሮውን ቀኖናዊ አስተሳሰብ መቀናቀንና፣ አዳዲስ የአስተሳሰብ ፈለጎችን መቅደድ አዲስ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ብቻ አልበቃም። የአውሮፓውም ማህበረሰብ፣ በተለይም የካቶሊክ ሃይማኖት በጣም የጠበቀ አስተሳሰብ የነበረውና ጨቋኝ ስለነበር እሱን የሚጋፈጥ በማርቲን ሉተር አማካይነት የሃይማኖት ተሃድሶ እንቅስቃሴ ማካሄድ አስፈለገ። ይህ በራሱ ማክስ ቬበር እንደሚለው ለአዲስ አስተሳሰብ ሁኔታውን በማመቻቸት የፕሮቴስታንት ስነ-ምግባር የሚባለው የስራና ሀብትን የማካበት ልምድ በመዳበሩ ለካፒታሊዝም ዕድገት ሌላ ዕምርታ ሰጠው። ይሁንና ግን ካፒታሊዝም በአሸናፊነት እንዲወጣ ሌላ እንቅስቃሴ መካሄድ ነበረበት። የአውሮፓውን ማህበረሰብ ከፍጹም ሞናርኪዎች አምባገነናዊ አገዛዝ አላቆ ርፑብሊኮችን ማቋቋም አስፈላጊ ሆነ። ይኸኛው እንቅስቃሴ በኢንላይትሜንት ወይንም በተገለጸለት ምህራዊ እንቅስቃሴ የሚወከልና ለሊበራሊዝም አስተሳሰብ መስፋፋት በሩን የከፈተ ነው። ከዚህ ጋር በመያያዝ መሬት የግል ሀብት መሆን፣ ይህ ጉዳይ ከህግ የበላይነት ጋር መያያዝ ለካፒታሊዝም መሰረት ሆነ። ይህ በየኤፖኩ የተፈጠረው አዳዲስ ሁኔታ ለመጨረሻ ጊዜ የፊዩዳሉን ስርዓት በማስወገድ ካፒታሊዝም በአሸናፊነት መውጣት ቻለ። የአውሮፓው ማህበረሰብም ዕድል ከእንግዲህ ወዲያ በካፒታሊዝም ምርታዊ እንቅስቃሴና ውስጠ-ኃይል የሚወሰን ሆነ። ይህ ጉዳይ እንደስርዓት በመወሰድና ተቀባይነት በማግኘት ህብረተሰቡ በዚህ የሚንቀሳቀስ ሆነ። በዚህ መልክ ዛሬ ካፒታሊዝም የሚባለውን ስርዓት እንድናይና፣ እንድንኖርበትና እንድንጠቀምበት ተገደድን። ይህ ስርዓት በአስተሳሰብ ስልት(Mode of thought)፣ በአመራረት ስልት(Mode of production)፣ በምርት ግኑኝነት(Production relationship)፣ በርዕዮተ-ዓለማዊና በባህላዊ(Mode of consumption and behaviour)  የሚገለጽና፣ ግለሰባዊ ድርጊትነትና ማንነት የተረጋገበጥ ስርዓት ነው። ለምን በሌሎች አገሮች ውስጥ እንደዚህ ዐይነቱ ስርዓት ሊፈጠር አልቻለም ለሚለው መልስ ለመስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሁንና ግን እኛ ስለስርዓት በምንታገልበት ጊዜ ከምን ተነስተና ወዴት እንደምንጓዝና፣ ምን ምን ችግሮች ከፊታችን ተደቅነው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥሩብን ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን። በሌላ ወገን ግን የታሪክን ሂደትና አስችጋሪ ጉዞ ሳይጠና እንዲያው በአቦሰጡኝ ተግባራዊ የሚሆን ስርዓት እንበለው ፖሊሲ ወደ መቀመቅ ውስጥ ይከተናል። አብዛኛዎች ህብረተሰቦችንም እየከተታቸው ነው። ስለሆነም ስለ ስርዓት ወይም ስለማህበረሰብ ግንባታ በምናወራበት ጊዜ በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ ማጥናት ያሉብን መዓት ነገሮች አሉ ማለት ነው። የፊዩዳሉን ስርዓት ወደ ካፒታሊዝም እንዴት እንደተሸጋገረ ለመገንዘብ ከታች የቀረበውን ስዕል መመልከቱ ነገሩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል።

 

 

 

 

 

የካፒታሊዝም ጉዞና የዕድገት ደረጃ፣ እንዲሁም በየኤፖኩ ያጋጠሙትን ችግሮች በደንብ ከመረመርንና ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን አንድን ማህበረሰብ ለማደራጀት ቀላል ይሆንልናል። ደረጃ በደረጃ መወሰድ ያለባቸውን ነገሮች ተግባራዊ ለማድረግና ህብረተሰብአችንን መልክ ለማስያዝ ይቀለናል። ዛሬ በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለው ችግር ስለካፒታሊዝም ዕድገት ያላቸው ግንዛቤና በምን ውስጣዊ ህግ እንደሚተዳደር ግራ መጋባት ህብረተሰቦቻቸውን እያተረማመሰባቸው ነው። ከፊዩዳሊዝም አስተሳሰብ ሳይላቀቁ ሶሻሊዝምንና የሊበራል ካፒታሊዝምን ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ መሯሯጥ፣ ህብረተሰቦች መስራት ያለባቸውን ነገሮች እንዳይሰሩና እንዳይገነቡ በመታገድ ህዝቦች በስርዓት እንዳይኖሩ እያደረገ ነው። በተለይም ዛሬ የተፈጠረው ውስን አስተሳሰብ፣ ካለሊበራል ዲሞክራሲና ካለገበያ ኢኮኖሚ ሌላ አማራጭ የለም እየተባለ የሚሰበከው አደገኛ ቅስቀሳ ደሃ የሆነውን ሰፊ ህዝብ መኖሪያ እያሳጣው ነው። በአገሩ ሰርቶ እንዳይኖር እያደረገው ነው። ህዝቦች በአገራቸው ውስጥ ህልማቸውን ዕውን እንዳያደርጉ ሁኔታው ሁሉ ጨልሞባቸዋል። ስለሆነም ከፊታችን አስቸጋሪ ነገር ተደንቅሮ ይገኛል ማለት ነው።

ይህንና በአጠቃላይ ሲታይ አሁንም ቢሆን አንድን ህብረተሰብ በአንድ የስርዓት ክልልና አመለካከት ብቻ ልናደራጀው በፍጹም አንችልም። ብዙ ስርዓቶች አንድ ላይ ተቀነባብረው ሊሄዱ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል። በሌላ ወገን ግን ይህ ሆነ ያኛው ስርዓት የግዴታ መታቀድ አለባቸው። ካለዕቅድ የሚሰራ ነገር የለም። የለም ይህ አያስፈልግም የምንል ከሆነ ደግሞ በቀጥታ ወደ ስርዓተ-አልበኝነት ነው የምናመራው ነው።  በአሁኑ በግሎባላይዜሽን ዘመን ሁሉ ነገር ልቅ መሆን አለበት፣ አገሮች ድንበሮቻቸውን ማጠር የለባቸውም፤ ለዓለም የገበያ ተዋናዮች ገበያቸውን ልቅ ማድረግ አለባቸው እየተባለ በሚሰበክበት ዓለም ውስጥ በተለይም እንደኛ የመሳሰሉሉ አገሮች ህዝባቸውን በስርዓት እንዳያደራጁ ሁሉ ነገር ታጥሮባቸዋል። በተለይም ኢንቬስተር ነን በሚሉና አማካሪዎች(Consulting Companys) ነን ብለው እዚህና እዚያ በመራወጥ ደካማ መንግስታትንና በጥሩ ዕውቀት ያልተገነቡ ፖለቲከኛ ነን ባዮችን የሚያታልሉ በብዛት በተሰራጩብት ዓለም ውስጥ፣ አንድን አገር በስርዓት ማዘጋጅት፣ ምርታማና ፈጣሪ ለማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ይታያል። ራሱ በዕድርና በዕቁብ መደራጀት ከሶሻሊዝም ጋር በሚገናኝበትና እንደመጥፎ ነገር በሚወሰድበት የኒዎ-ሊበራሊዝም ዓለም ውስጥ ሁሉም ነገር ካለ ዕቅድና ካለስርዓት ልቅ በሆነ መልክ ብቻ ነው መስራት ያለበት። ይህ ዐይነቱ፣ ሀቀኛውንና ሳይንሳዊ የአሰራርና ተፈጥሮአዊ ህግን የሚቀናቀን ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከት በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ራሱ ምሁር ነኝ የሚለው ጥያቄ መጠየቅ ተስኖት አሁንም የገበያ ኢኮኖሚ እያለ ሲጮህ ይሰማል።

አብዛኛው ታጋይ ወይም ምሁር ባይ፣ ወይም ለአገሬ እቆረቆራለሁ የሚለውና እዚህና እዚያ የሚጮኸው በወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ በአለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት በአገራችን ምድር የተዘረጋውን ስርዓት ለመመርመር ተስኖት የሚሆን የማይሆን ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም ነገር ሲናገር ይሰማል። ከማንኛውም ታጋይ ወይም ምሁር ባይ በአገራችን ምድር ውስጥ ምን ዐይነት ስርዓት እንደተዘረጋ የተሰጠ መግለጫ በፍጹም የለም። ነገሮች ሁሉ በፖለቲካ ክልልና ከስልጣን ጋር ተያይዘው ይታዩ ስለነበር በህዝባችን ላይና በጠቅላላው የህብረተሰብአችን አወቃቀርና አረማመድ ላይ የተዘረጋው መጥፎ ስርዓት ለወደፊቷ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የመገንባት ጉዳይ የቱን ያህል ዕንቅፋት እንደነበርና እንደሚሆን ግንዛቤ ውስጥ የተገባ አይደለም። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በግሎባል ካፒታሊዝም ስር የወደቀችና የምትታሽ፣ እንዲሁም ሀብቷ የሚዘረፍባት አገር ነች። ልክ በቅኝ ግዛት የአስተዳደር ዘመን በሚመስል ህዝቦቿ ወደ ባርነት ስራ የተሰማሩባት ሁኔታ በአንዳንድ ቦታዎች በግልጽ ይታያሉ። የሰሊጥ ተከላ መስፋፋት፣ የሸንኮራ አደጋ በብዛት ተተክሎ ስኳር ማምረት፣ የአበባ ተከላና የቡና ምርት ልዩ ዐይነት የገበያ ልውውጥ ተቋቁሞ የህዝቡ አትኩሮ በዚያው ላይ ተወስኖ እንዲቀር ማድረግ፣ የግሎባል ካፒታሊዝም ካዋቀረው አዲስ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። በግሎባል ካፒታሊዝም ስትራቴጂ እንደኛ ያሉ አገሮች ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ(Plantation Economy) መለወጥ አለባቸው። ህዝባችን ፍራፍሬ እየተከለ፣ ሽንኮራ አገዳና ሌሎች የእርሻ ምርቶችን እያለማና አያስፋፋ የኢንዱስትሪ አገሮችን መመገብ አለበት። በዚህ አዲሱ ስትራቴጂ መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በምንም ዐይነት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ በኢንዱስትሪ የሚንቀሳቀስ የውስጥ ገበያ መገንባት የለባቸውም። ውብ ውብ ከተማዎችን በመገንባትና፣ በልዩ ልዩ የመገናኛና የመመላሻ ዘዴዎች በማገናኘት ህዝቦቿ ተደስተውና እንደ አንድ ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው መኖር የለባቸውም። ይህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና የአገር ግንባታ ለዘረፋና አንድን ህዝብ አደኽይቶ መኖር ስለማያመች ግሎባል ካፒታሊዝም እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች እየታሹና ፍርፋሪ እየተወረወረላቸው መኖር እንዳለባቸው ወስኗል። በዚህ መልክ በወያኔ አገዛዝና በግሎባል ካፒታሊዝም መሀከል በተመሰረተው ያልተቀደሰ ጋብቻ ህዝባችን ዘለዓለሙን በድህነት እንዲኖር ተረግሟል። ዛሬም ይህ ዐይኑነቱ ሁኔታ ቀትሏል። የዚህ ሁሉ መግለጫው ደግሞ በአገሪቱ ከተማዎች ውስጥ የቆሻሻ ዕቃና ልብስ መሸጫ ቦታዎች መስፋፋት ነው። ይህ ዐይነቱ የቆሻሻ የሸቀጥ ማራገፊያ፣ ከቻይና የሚመጣ በርካሽ ጉልበት የተመረተ ልብስና ጫማ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የቁሳቁስ ነገሮች መሸጥና የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ምርት እንቅስቃሴ መዳከምና፣ ምርታማ ወዳልሆነና የማባዛት ኃይል ወደሌለው የምርት እንቅስቃሴ ላይ መሰማራት፣ የአገልግሎት መስኩ ከፍተኛውን ቦታ መያዝና ህብረተሰቡን ማዘበራረቅ የስርዓቱ ልዩ ባህርዮችና መግለጫዎች ናቸው። ከዚህ ስንነሳ የአገዛዙ ርዕይ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚገለጽ ሳይሆን፣ ግራ የገባው ግን ደግሞ በዘረፋ ላይ ተመስርቶ የህብረተሰቡን ውስጣዊ-ኃይልና አንዳንድ ታታሪ ሰዎችን የሚጋፈጥና ለውጭ ገበያ ልቅ አድርጎ የህብረተሰብአችንን የማምረት ኃይል የሚያዳክም ነው። በሌላ አነጋገር፣ የዛሬውን የኢትዮጵያ የማህበረሰብ አወቃቀር በአንድ በጠራ አመለካከትና አገላለጽ መግልጽና መተንተን ያስቸግራል። እንደዚህ ዐይነት ስርዓት ነው በአገራችን ምድር የሰፈነው ብሎ መናገር ያዳግታል።  ይሁንና ግን የተዘበራረቀና ወዴት እንደሚያመራ ግልጽ ያልሆነ ሁኔታ በጉልህ ይታያል።

ከዚህ በመነሳት እዚህም ሆነ እዚያ ተደራጅቶ እታገላለሁ የሚለው ኃይል ሁሉ ለምን ዐይነት ስርዓት እንደሚታገል ቢያስታውቅ ለመከራከርም ሆነ፣ ለመማርና ለማስተማር መንገዱ ክፍት ይሆናል። የለም ዝምብለህ አፍህን ዘግተህ ተቀመጥ፣ እኛ ስልጣን ስንይዝ የዚያን ጊዜ ለምን ስርዓት እንደምንታገል በተግባር እናሳይሃለን የሚባል ከሆነ ይህ ዐይነቱ አካሄድ እጅግ አደገኛና የጮሌዎች ጉዞ ነው። ለኛ ለነቃን ኃይሎች ግን እንደዚህ ዐይነቱ የጮሌዎች አካሄድ አይጥመንም፤ ዝም ብለንም እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ህብረተሰብአችን ወደመቀመቅ ውስጥ ሲገባ ማየት አንችልም። ህሊናችንም አይፈቅድም። ፊደል የቆጠርን ስለሆንና የታሪክም ኃላፊነት ስላለብን ለምን ዐይነት ስርዓት ነው የምትታገሉት? እያልን ከመወትወት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም። በመሆኑም ሁሉንም፣ ለብሄረ-ሰብ ነፃነትም ሆነ የብሄራዊ አጀንዳ አለን ብለው የሚታገሉትን ኃይሎች ለምን ዐይነት ስርዓት እንደሚታገሉ ቢያስረዱንና ግልጽ ቢያደርጉሉን የትግል አቅጣጫው መስመር ይይዛል ብዬ እገምታለሁ።

ያም ሆነ ይህ በጭንቅላታችን ውስጥ አንዳች ዐይነት ስዕል እንዲኖረን ከዚህ በታች ያሉትን ግራፊኮች መመልከቱ አንድ ህብረተሰብ በምን መልክ መደራጀት አለበት ለሚለው ተቀራራቢ መልስ ሊሰጠን ይችላል። ይሁንና ግን እዚህ ላይ በግራፊኩ ውስጥ እንደ የሀብት ቁጥጥር ጉዳይንና ክፍፍልን የመሳሰሉት አልተካተቱም።

ህብረተሰብ እንደኔት-ወርክ

 

 

አንድ ህብረተሰብ እርስ በራሳቸው በሚደጋገፉ ንዑስ-ስርዓቶች ተዋቅሮ የሚካሄድ ነው። አንደኛው ሌላውን ስለሚፈልገው አንደኛው በሌላው ላይ ጭነት አደርጋለሁ ቢል መዛባትና መዘበራርቅ ይፈጠራል። በተለይም በዚህ ሂራርኪ በሚመስል የህብረተሰብ አወቃቀር ውስጥ ፖለቲካዊ አወቃቀር ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የፖለቲካው ስርዓት በዕውቅና በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተና፣ እንዲሁም ደግሞ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና ባላቸው ሰዎች የማይመራ ከሆነ ሌሎች ንዑስ ክፍሎች በስነስርዓት ሊደራጁና ህብረተሰቡ እንደማህበረሰብና እንደህብረተሰብ ሊደራጅና ታሪካዊ ስራዎችን ሊያከናውን በፍጹም አይችልም። ስለሆነም ስለአንድ ስርዓት ወይም ህብረተሰብአዊ አወቃቀር በምናወራበት ጊዜ የግዴታ የፖለቲካውን መስክ ማስተካከል ያሰፈልጋል። „አሳ መግማት የሚጀምረው ከጭንቅላቱ ነው“  እንደሚባለው አነጋገር፣ የተበላሸ የፖለቲካ ስርዓት ለዕድገት አያመችም። ከዚህ በመነሳት ነው ሌሎች ነገሮችን ደረጃ በደረጃ ማደራጀትና እንደየአስፈላጊነታቸው ማስተካከል የሚቻለው። ስለሆነም ምን ዐይነት ፖለቲካና ምን ዐይነት አደረጃጀት የህብረተሰብአችንን ችግር ሊፈታው ይችላል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር።

የፖለቲካ አደረጃጀትና ትርጉም ጉዳይ!

አንድ በሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ የተቀረፀና እንደፎርሙላ የተወሰደ አነጋገር አለ። ይኸውም የግዴታ የመደብለ-ፓርቲ ስርዓት መኖርና፣ በየአራት ዐመቱ ምርጫ ማድረግ ለአገራችን መፍትሄ ሊሆን ይችላል ተብሎ ታምኗል። እንደሚታወቀው የአገራችን ችግር ውስብስብ ነው። ኢኮኖሚው የተዘበራረቀና ህብረተሰብአችንን ሊመግብና ለህዝባችን አለኝታ ሊሆን የሚችል አይደለም። የባህሉም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ነገሮች በደንብ የተደራጁ አይደሉም። ይህ ዋናው መሰረታዊ አስቸጋሪ ጉዳይ ሲሆን፣ ባለፉት ሃያ ሰምንት ዐመታት በተለይም ኮሙኒዝም የሚባለው ስርዓት ከፈራረሰ በኋላ በምስራቅ አውሮፓ ይኸኛውን ወይም ያኛውን ርዕዮተ-ዓለም እንከተላለን የሚሉ ፓርቲዎች እንደ አሸን በፈለቁበትና የፖለቲካ ተዋናዮች በሆኑበት አገሮች ፓርቲዎቹ በደንብ አለመደራጀታቸው ብቻ ሳይሆን ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ህብረተሰቦቻቸውን የባሰውን ሲያዘበራርቁ ይታያል። አብዛኛዎቹም በራሳቸው ኃይል የሚንቀሳቀሱ ሳይሆኑ የዚህ ወይም የዚያኛው ኃያል መንግስት ትዕዛዝ ተቀባይ በመሆን ችግር ፈቺዎች ከመሆን ይልቅ ችግር ፈጣሪዎች ሆነዋል። አንዳንዶቹ ወደማፊያነት የተለወጡ ነው የሚመስለው። ቡልጋሪያንና ሩሜኒያን መመለክቱ ጥሩ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል። በዚህም የተነሳ እነዚህም ህዝቦችም ሆነ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ህዝቦች የየፓርቲዎችና አገዛዝ ነን በሚሉ ቁራኛ ውስጥ ወድቀዋል።ህዝቦች የየአገሮቻቸው ባይተዋር በመሆን ዝምብለው እንዲመለከቱ ተገደዋል። በመሆኑም በእነዚህ የድሮ ምስራቅ አውሮፓ የኮሙኒስት አገሮች ተግባራዊ የሆነው የገበያ ኢኮኖሚ ድህነትን ፈልፋይ ከመሆን በስተቀር ያመጣው ፋይዳ ነገር የለም።

ይህ ችግር ከምን የመነጨ ነው? እንደ አገራችን ሁኔታም የእነዚህ አገሮች መሰረታዊ ችግር በሬናሳንስና በኢንላይትሜንት እንቅስቃሴ ውስጥ ስላላለፉ ከውስጥ ህብረተሰቡን ሊመራ የሚችል ምሁራዊ ኃይል ሊፈልቅና ሊዳብር አልቻለም። ከበርቴያዊ የሆነ ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና በካፒታሊዝም ሎጂክ ላይ የተገነባ ኢኮኖሚም መፈጠር ስላልቻለ ብስለትና ጥበብ የተሞላበት ፓለቲካ ማካሄድ የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ስለሆነም በአገራችን እንደሚታየው ዐይነት በነዚህም አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ምሁራዊ ክፍተትና የመደባዊ አደረጃጀትና ዕድገት ችግር በጉልህ ይታያል። ስለዚህም አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች አንድ የፖለቲካ ድርጅት ማድረግ ያለበትን መንሳቀሻ መሰረተ-ሃሳቦች ያሟሉ አይደሉም። ብዙዎቹም ይህንን ወይም ያኛውን የፓርቲ ስም ቢይዙም ለምን ይህንን ወይም ያኛውን ስም እንደመረጡም የሚያውቁ የሚመስሉ አይደሉም። የሶሻል ዲሞክራቲክ ፕሮግራም ይዞ የሚንቀሳቀሰው ምርጫ አሸንፎ ስልጣን በሚይዝበት ጊዜ ዕልም ያለ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲያራምድ ይታያል። ህዝቡን የባሰውን ወደድህነት ይገፈትረዋል። በዚህም ምክንያት የድሮዎቹ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ያልተረጋጋና ህዝቦችን የስራ መስክ ዕድል መስጠት ያልቻለ ነው። አብዛኛዎቹ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች አገዛዞች በራሳቸው ማድረግ የሚገባቸውንና የሚችሉትን ማድረግ ተስኗቸው የአውሮፓው አንድነት የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ መጫወቻ ሆነዋል ማለት ይቻላል።

ወደ አገራችንም ስንመጣ ያለው ችግር ይህንን ይመስላል። አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ከፕሮግራም አልፈው የሄዱና የሚሄዱ አይደሉም። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍልስፍናቸውም ግልጽ አይደለም። በዚህም ምክንያት ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደሚታገሉ ግልጽ አይደለም። እንዲያው በደፈናው ሁሉም ለገበያ ኢኮኖሚ የሚታገልና ጥብቅና የቆመ ነው የሚመስለው። የገበያው ኢኮኖሚ ደግሞ በምን መልክ መዋቀር እንዳለበትና፣ እንዴትስ ደረጃ በደራጃ የህብረተሰብአችንን ችግር እንደሚፈታ ግልጽ ሆኖ አልቀረበም።

በእኔ ዕምነትና ምርምር ብዙዎች በፓርቲ ደረጃ ተደራጀን የሚሉት በምሁራዊ ክንዋኔና የክርክር ሂደት ውስጥ አልፈው የተዋቀሩ አይደሉም። ይህም ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ የፖለቲካ ክፍተትና የተዘበራረቀ የህብረተሰብ አወቃቀር ውጤቶች እንጅ በዕምነትና በርዕይ ዙሪያ ከረዥም ጊዜ ክርክርና ጥናት በኋላ የተቋቋሙ አይደሉም። የትችትን ባህልና ነገሮችን ከሁሉም አንፃር ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ የመከራከር ልምድ የላቸውም። በዚህም ምክንያት አንድኛው በአጋጣሚም ሆነ በምርጫ ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ የህብረተሰብአችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት እንደሚሳነው ከአሁኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ሌላው የእነዚህ በአገራችን እንቀሳቀሳለን የሚሉ ድርጅቶች ችግር በብሄራዊ ነፃነታችን ላይና፣ በጠቅላላው ስለዓለም ፓለቲካና የኢኮኖሚ አወቃቀር ያላቸው ግንዛቤ ግልጽ አይደለም። ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እንደሚካሄድ በፍጹም የሚያውቁት ነገር የለም።

አብዛኛዎቹ የዓለምን የተወሳሰበ የፖለቲካ ሁኔታ በየዋህነት መነፅር ነው የሚመለከቱ እንጂ፣ በምሁራዊ ትንተናና ግንዛቤ ቀረብ ብለው በመመልከት ምን ምን ዐይነት ፖለቲካ መከተል እንዳለባቸው የተረዱ አይመስሉም። ብዙዎቹ ፓርቲዎች የራሳቸው የሆነ ኢንስቲቱሽንና፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንዲሁም የልዩ ልዩ ዘርፎች አማካሪዎች ያሏቸው አይመስልም። ይህ ዐይነቱ የአደረጃጀት ባህልና የኤክስፐርቶች ስራ ባለመኖሩ፣ ስራቸውና ፖለቲካዊ አረማመዳቸው ግብታዊ ነው። ከሌላ የሚመጣ ገንቢ የሆነ ትችታዊ አቀራረብና መፍትሄን ለመቀበል የተዘጋጁ አይደሉም። እንዲያውም ከአገራቸው ሰው ይልቅ የፈረንጁን ምክር የበለጠ የሚያዳምጡና በሱ የሚመሩ ነው የሚመስለው። ይህ ዐይነቱ አካሄዳቸው በብሄራዊ ነፃነታችንና በአገር ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው መገንዘብ ይቻላል። በውስጣቸውም ሰፊ ውይይት እንደማይካሄድ መናገር ይቻላል። ስለዚህም እንመራዋለን የሚሉትን ህዝብ በምን ፍልስፍና ላይ ተመስርተው እንደሚመሩትና፣ ለምን ዐይነቷ ኢትዮጵያ እንደሚታገሉና ምንስ ዐይነት ህብረተሰብ መገንባት እንዳለበቸው ሲጠቁሙን አይታይም።

ወደ ጠቅላላው ህብረተሰብአችን ስንመጣ ደግሞ ሰፋ ያለ የሲቪክ ማህበረሰብ እንቅስቃሴም ሆነ ባህል የለም። በተለያዩ መስኮች ህዝባችን ሲጠቃ ይህንን የሚከላከልና ተግባራዊ እንዳይሆን በከፍተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ የሚያደርግ የለም። ከአንዳንዱ በስተቀር ምሁር ነኝ የሚለው አያገባኝም በማለት ህዝባችንን ለብዙ አስቸጋሪና አደገኛ ነገሮች አጋልጦ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠ ነው የሚመስለው። ለባህላችን መከስከስ ተከላካይ የሆነ የሲቪክ ማህበረሰብ እንቅስቃሴ የለም። ህዝቡ መሬቱ ሲነጠቅ እሱን ለማገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ የለም። በከተማው ውስጥ ህዝቡ ካለአግባብ ከመሬቱና ከቤቱ በልማት ስም ሲፈናቀልና፣ ለህብረተሰቡ የማይጠቅሙ ህንፃዎች ሲሰሩ እሱን ለመከላከል የሚደረግ ትግል የለም። የተበላሸ የአርከቴክቸር አሰራር ሲስፋፋና ጌቶ የሚመስሉ ግንቦች እዚህና እዚያ  ሲገነቡ በሰው፣ በተለይም ደግሞ በታዳጊው ትውልድ ላይ ሊኖራችው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የሚቃወምና የሚያጋልጥ የለም። በአሜሪካ የጂን ላቦራቶሪ የተዳቀለ ስንዴና በቆሎ የአገራችን ገበሬ ሰለባ ሲሆን ይህንን የሚያጋልጥ የለም። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የዚህን አደገኛነት የተገነዘቡ አይመስልም። ከዚህ ባሻገር የሙያ ድርጅቶች፣ የገበሬ ማህበራትና የሴቶችና የወጣቶች ድርጅቶች የሉም። ባጭሩ ህብረተሰብአችን ችግሩንና ብሶቱን የሚያሰማበትና የሚወያይበት እንዲሁም በጋራ የሚጋፈጥበት መድረክ የለውም።

ወደ መንግስት መኪና ስንመጣ በብዙዎቻችን ዘንድ ፊዩዳላዊ የሆነ አመለካከት ነው ያለው። ለምሳሌ የአውሮፓን የህብረተሰብ ታሪክና የመንግስት አወቃቀር ስንመለክትና፣ በዚህም ዙሪያ የተደረገውን የመንግስት ቲዎሪ ስናነብ የምንገነዘበው በየጊዜው ብቅ ያሉት ምሁራን የመንግስት አወቃቀርን ምንነትና፣ መንግስት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚኖረውን ሚና በየኤፖኩ ክርክርና ጥናት ሲያደርጉ ነበር። ከእነ ፕላቶ ጀምሮ ከክርስቶስ ልደት ከስድስተኛው ክፍለ-ዘመን በኋላ ብቅ ያሉት ቀሳውስትና ፈላስፋዎች ስለመንግስት ምንነትና ሚና ያደርጉ የነበረውን ክርክራና ጥናት መመልከት ይቻላል። የሁሉም አቋም ታይራኖችን ወይም አምባገነኖችን አጥብቆ የሚቃውምና የህዝብን ማዕከለኛ ቦታ ያስቀመጠ ከፍተኛ መንግስታዊ አመለካከት ነው። በሌላ አነጋገር፣ አንድ መንግስት የህዝቡን ደስታ የሚያሰቀድምና፣ ለዚህም የሚታጋል ታሪክ አሰሪ መድረክ መሆን እንዳለበት ግንዛቤ ውስጥ የተገባና እንደመሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታም የተወሰደ ነው። በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን በጥበባዊ መንግስት ምስረታ አስፈላጊነት ዙሪያ የተካሄደውን ጥናት መመልከት ይቻላል። የእነሺለርና ሀርደር የጥበባዊ መንግስት ፍልስፍና ህዝብን በማዕከላዊ ቦታ ያስቀመጠ ብቻ ሳይሆን፣ መንግስትና ህዝብ፣ መንግስትና ህብረተሰብ ተለያይተው መታየት የሌለባቸውና፣ መንግስትም የብልጽግናውን መንገድ ቀያሽ እንደሆነ ነው የሚያስተምሩን። ይህም ማለት በአውሮፓ ውስጥ የመንግስት አወቃቀር በጥናት ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን ከታች ወደላይ ኦርጋኒካሊ እየዳበረና እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በካፒታሊዝም ውስጠ-ኃይል(dynamism) ጥገናዊ ለውጥን እየተላበሰ የመጣ ነው። ማለትም ለካፒታሊዝም አጠቃላይ የሀብት ክምችትና ስርዓቱ ካለብዙ መወዛገብ እንዲሰራ ተብሎ የተዘጋጀ ነው። ይሁንና በፓርቲዎችና በመንግስት መኪና መሀከል ግልጽ ልይነት አለ። የመንግስት መኪና በአንድ ፓርቲ ስር የወደቀና ወደ አገር አፍራሽነት የተቀየረ አይደለም። በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ በሎቢይስቶች ቁጥጥር ስር ያለ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በአሸባሪነት ስም ጦርነትን የሚያካሂድና ደካማ አገሮችን የሚያተራምስ ነው። በተለይም የሚሊታሪውና የስለላ ድርጅቶቶች በራሳቸው የሚንቀሳቀሱና ከፓርሊያሚንት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ናቸው።

ለማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች ዐይነት መሰረታዊ ለውጥ ይምጣ ከተባለ አሁን ባለው የመንግስት አወቃቀር ወደፊት መንቀሳቀስ አይቻልም። ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያሉት ችግሮች በሙሉ እኛም አገር ውስጥ አሉ። የመንግስቱ መኪና በውጭ የስለላ ኃይል የተተበተበና ለህልውናችንና ለብሄራዊ ነፃነታችን ተቀናቃኝ ነው። በመንግስትና በህዝቡ እንዲሁም በጠቅላላው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል ያለው መተሳሰብና መደጋገፍ በግልጽ የተቀመጡና፣ በየጊዜው እየተጠኑ የሚሻሻሉ አይደሉም። የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ብሄራዊ ነፃነትን የሚያስከብር መንግስታዊ አደረጃጀትና አወቃቀር አይደለም በአገራችን ምድር ያለው። አሰራሩና አወቃቀሩ ወደ ኋላ የቀረ ነው። በየሚንስትሪዎች ውስጥ የተቀመጡት ባለስልጣናት በውጭ ኃይሎችና አማካሪዎች የሚጠመዘዙ እንጂ ለአገራችን ዕድገትና ህልውና የቆሙ አይደሉም። ይህ ሁኔታ በአለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት እየተበላሽ የመጣና፣ የመንግስቱ መኪና የተለያዩ የውጭ ኃይሎች መፎካከሪያ መድረክ ሆኗል ማለት ይቻላል። በአገራችን የሚታየው የሃይማኖት፣ የብሄረ-ሰብ ውዝግብና፣ በአማርኛ ቋንቋችን ላይ የተደረገው ዘመቻ የግዴታ ከውጭ ኃይሎች የተንኮል ሸረባ ጋር የተያያዘ ነው። ህብረተሰብን በመበወዝ፣ በማከረባበትና ወደ ብጥብጥ እንዲያመራ በማድረግ የተካነችው እንግሊዝ ተቀዳሚውን ቦታ በመያዝ ህብረተስብአችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዲያመራ የማታደርገው ነገር የለም። አሜሪካም ከዚህ ያላነስ ርኩስ ጨዋታ እንደሚጫወት ግልጽ ነው። ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ መንግስታትም በእንደዚህ ዐይነቱ ያለመረጋጋትና የተንኮል ስራ የሚጫወቱት ሚና ብዙ የሚጻፍለት ነው። ለምንድነው አነዚህ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት ይህን ዐይነቱን ተንኮል የሚሸረቡት?  ነገሩን ለመረዳት ብዙም መጨነቅ አያስፈልግም። እነዚህ ኃይሎች ወደዚህ ርኩስ ስራ ተሰማርተው ህዝብ እንዲበጣበጥ የሚሸርቡት ተንኮል አንድ ህዝብ በውዝግብ ዓለም ውስጥ ከኖረና ወደ ጦርነት ካመራ መስራትና ማድረግ ያለበትን ታሪካዊ ድርጊት እንዳያከናውን ይቆጠባል። ጭንቅላቱ በማይሆኑ ነገሮች ስለሚጠመድ ለማሰብና ለመፍጠር፣ እንዲያም ሲል አገር ለመገንባት ጊዜ ለማግኘት በፍጹም አይችልም። ስለሆነም በታሪክ እንደታየው ታታሪ አመራር ስልጣን ላይ ካለ እሱን ቶሎ ብለው ለማጥፋት ይጣደፋሉ፤ ካለያም ደግሞ እንደዛሬው ሁኔታው ሲያመቻቸው በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሰርጎ በመግባት ብጥብጥ እንዲነሳ ያደርጋሉ። ይሁንና የውጭ ኃይሎች በአገራችን ህልውና ውስጥ ገብቶ መፈትፈትና ወደብጥብጥ እንዲያመራ ማድረግ በፓርቲ ደረጃ ተደራጀን በሚሉት ዘንድ ግንዛቤ ውስጥ የተገባ አይመስልም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ እነሱን አምላኪ በመሆን ብሶታቸውን ለማሰማት ሲሯሯጡ ይታያል። አብዛኛዎቹ ፓርቲዎችም ሆነ የታወቁ ግለሰቦች ካለአሜሪካ ቡራኬና ፈቃድ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ነው የሚያወሩልን። አሜሪካ የሁሉ ነገር አድራጊና ፈጣሪ ተደርጎ ነው የሚተረክልንና አምነንም እንድንቀበል የሚደረገው። እነዚህ ድርጅቶችም ሆነ አንዳንድ ግለሰቦች ያልገባቸው ነገር ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን ነው። ዛሬ ኃያል የሆነው መንስግስት ነገ በሌላ እንደሚተካ በፍጹም አልገባቸውም። ከዚህ በተለየ ግን የአሜሪካንን የበላይነት አምነው ሲቀበሉና ካለሱ ፈቃድ ምንም ነገር መስራት አይቻልም ብለው ሲሰብኩ እራሳቸው ሰው መሆናቸውን ይዘነጋሉ። ሁሉም ሰው በአምላክ ምስል ነው የተፈጠረው የሚለውን የመጽሀፍ ቅዱስ አባባል ይስቱታል። ፈልግ ታገኛለህ፤ ጠይቅ መልስም ታገኛለህ፤ አንኳኳ በሩ ይከፈትልሃል፤ እንድታይ ዐይን ሰጥቼአለሁ፤ የምትመራመርበትንና የምትፈጥርበትም ጭንቅላት አለህ የሚለውን ግሩም ምሁራዊ አባባል የዘነጉ ይመስላሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዐይነት አስተሳሰባቸው የአገራቸውን ታሪክና እናቶቻችንና አባቶቻችን ብሄራዊ ነፃነታችንን ለማስከበር ያደረጉትን ትግልና የከፈሉትን መስዋዕትነት ይዘነጋሉ።

ከዚህ የተወሳሰበው ሁኔታ ስንነሳ የፖለቲካው አደረጃጀት ግልጽና በአንዳች ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ወደ ከፍተኛ ምሁራዊ ውይይትና ክርክር ማምራት አለበት። የፖለቲካው መድረክ ለማንም ተደራጀሁ ለሚል ሁሉ ክፍት መሆን የለበትም። ተደራጀሁ የሚል በሙሉ ፍልስፍናውንና ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልገውን ፖሊሲ በግልጽ ወደ ወጭ አውጥቶ ለክርክርና ለውይይት ማቅረብ አለበት። ማስረዳትና ማስተማር አለበት። በሌላ ወገን ግን የአገራችን የተወሳሰበ ችግር በአንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ትከሻ ላይ ብቻ የሚወድቅ አይደለም። ከስልጣን ሽኩቻና እሽቅድምድሞሽ ባሻገር ሁሉም ኃይሎች ከአዲስ አበባ እስከሌሎች ክፍላተ-ሀገራት ወይም ክልሎች ድረስ የሚካፈሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ስለሆነም በአገራችንም ምድር በክልል ደረጃ ተዘረጋ የተባለው ፌዴራላዊ አስተዳደር የሚባለው ፈርሶ ተግባራዊ በሚሆን በክፍለ-ሀገራት ደረጃ ቢዋቀር ሀብትን ለማንቀሳቀስና አገርን ለመገንባት ይቀላል። አብዛኛዎቹ በብሄር ደረጃ የተዋቀሩ ክልሎች ክልሎቻቸውን ለማሰተዳደርና አዲስ ሀብት ለመፍጠር ችሎታ ስለሌላቸው አዲስ የፖለቲካ ባህል መዳበርና አዳዲስ ኢንስቲቱሽኖች መቋቋም አስፈላጊና ወሳኝ ናቸው። ሰፋ ባለና በሁሉም አኳያ በሚገለጽ በከፍተኛ ዕውቀት በተካነ ኢንስቲቱሽናዊ አወቃቀር ብቻ ነው አንድን አገር መገንባት የሚቻለው። የሰውን ኃይልና የተፈጥሮን ሀብት ማንቀሳቀስና ለአገር ግንባታ አውሎ ህዝቡ እንዲጠቀመው ለማድረግ የግዴታ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ታታሪና ማሰብ የሚችል ኃይል እየተኮተኮተ ቦታ መያዝ አለበት። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ዛሬ የተስፋፋውን ሙስናዊ አስተዳደርና የሀብት መባከንን፣ እንዲሁም የውጭ ኢንቬስተር ነን ባዮችን ዘረፋና አገር አጥፊነት መቋቋም የሚቻለው።

ለዚህ ቁልፉ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ነፃነት ከአላንዳች ገደብ መስፈን አለበት። ዲሞክራሲ ሲባል እንዲያው በየአራት ዐመቱ ምርጫ እየተካሄደና ወካይ ነን ባዮችን እያዩ መኖር ሳይሆን በእርግጥም ህዝቡ ደረጃ በደረጃ ራሱ የሚደራጅበትንና ሃሳቡን እየገለጸ በአገር ግንባታ ውስጥ የሚሳተፍበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የመሳተፍና የሃሳብ ገለጻ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዐይነቱ ዲሞክራሲ ተወካይ ነን የሚሉትንም የመቆጣጠሪያ መሳሪያ መሆን አለበት። እንደ ኢትዮጵያ ባለ በብዙ ሺህ ችግሮች በተተበተበት አገርና፣ ድህነትና የኑሮ ምስቅልቅልነት አፍጦ አግጦ በሚታይበት አገር ችግሩን በተወካዮች ብቻ መቅረፍ አይቻልም። ዲሞክራሲን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የግዴታ ህዝቡ እንዲማርና እንዲያውቅ፣ እንዲሁም ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ ስፋ ያለ የትምህርት ተቋማት መዘርጋት አለበት። በተለይም ተራው ህዝብ ከስራ በኋላ ማታ ማታ እየሄደ አዲስ ዕውቀት የሚቀስምበት ህዝባዊ ባህርይ ያላቸው የሙያና የቀለም እንዲሁም ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን የሚሰጡ የህዝብ ትምህርትቤቶች መቋቋም አለባቸው። በተጨማሪም በቀላል ቋንቋ የማማሪያ መጽሀፎችን እያዘጋጁ ማደል ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር ዕድገትና ተቻችሎ መኖር የግዴታ ዕውቀት መሰረታዊ ቦታን ይይዛል። ዕውቀት ባልተስፋፋበት፣ ጥቂት ተማርን የሚሉ ስልጣን በጨበጡበትና የፈለጋቸውን ፖሊሲ እያወጡ ተግባራዊ በሚያደርጉብት አገር የመጨረሻ መጨራሻ አለመረጋጋትና ድህነት ይፈጠራሉ። ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ባልሰፈነባቸውና ዕውቀት ባልተስፋፋባቸው አገሮች የምንመለከተው ሀቅ መመሰቃቀልንና ብጥብጣን፣ የመጨረሻ መጨረሻም መሰደድን ነው። ስለዚህም የህዝቡ ተሳትፎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለዲሞክራሲያዊ አገር ግንባታ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል።

ከዚህ ስንነሳ የፖለቲካን ምንነት ወይም ተግባር በመጠኑም ቢሆን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በመሰረቱ ፖለቲካ የአንድን አገር ህዝብ ማስተዳደሪያ መሳሪያ ነው። ፖለቲካ አንድን አገር ጥበባዊ በሆነ መልክ ለማስተዳደር፣ በህብረተሰብ ውስጥ ያሉና ሊከሰቱ የሚችሉ ቅራኔዎች እንደየሁኔታው ሊፈቱ የሚችሉበትን ዘዴ መፈለጊያ መሳሪያ ነው። ፖለቲካ በመሰረቱ ለጥቂቶች የተሰጠና የሚሰጥ፣ አንድን አገር እንደፈለጋቸው ሊበውዙበት የሚፈቀድላቸው መሳሪያ አይደለም። ፓለቲካ የአገር ማስተዳደሪያ ጥበብ እንደመሆኑ መጠን አንድ ህዝብ በትክክለኛ አመራር ታሪክን እንዲሰራ ማዘጋጃ መሳሪያ ነው። ይህ አስተሳሰብ የግዴታ ጭንቅላት ውስጥ መያዝ አለበት። በሌላ ወገን በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ያለው የፖለቲካ እሰተሳሰብ ግንዛቤ የጥቂቶች ግል ሀብት ይመስል ህብረተሰብን ማከረባበቻና ማዘበራረቂያ መሳሪ ወደመሆን ተለውጧል። ለዚህ ዋናው ምክንያት በየአገሮች ውስጥ የፖለቲካ ባህል አለመዳብር፣ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖር፣ ከዚህም በመነሳት ጥቂት ፖለቲከኛ ነን ባዮች እንደ አምላክ የሚቆጠሩበትና ያሻቸውን ለማድረግ የተፈቀደላቸው ይመስል ህገ-መንግስትና ህዝብ ሳይፈቅድ ከሌላ መንግስት ወይም ኩባንያ ጋር ስምምነት በመፍጠር የአገርን ጥሬ ሀብት የሚቸበችቡበት፣ የጦር ካምፕ የሚሰጡበትና የስለላ መረብ እንዲዘረጋ በማድረግ ነጻነት እንዳይኖር የሚያደርጉ ሁኔታዎች በብዙ የአፍሪካ አገሮችና በእኛም አገር ተስፋፍተዋል። ይህ ዐይነቱ አመለካከት እስካለና፣ አንዳንድ ግለሰቦች ተሰባስበው ፓርቲ የሚባል ነገር ከመሰረቱ በኋላ ቡራኬ ለማግኘት ሲሉ ወደ ትላልቅ ኤምባሲዎች ዘንድ የሚያመሩና ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ ከሆነ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ከመጀመሪያውኑ የፖለቲካ ትርጉም ምን እንደሆነ አልገባቸውም ማለት ነው። የውጭና የውስጥ ፖለቲካ የሚባል ነገር ቢኖርም፣ ለፖለቲካ ስልጣን እታገላለሁ፣ ህዝብ አስተዳድራለሁ፣ በዚያውም ታሪክ እንዲሰራ አደርጋለሁ የሚል በመጀመሪያውኑ መረዳት ያለበት ለአገሩና ለህዝቡ ተገዢና ተጠሪ መሆኑን ነው። ይህ ግልጽ ሲሆን ብቻ በፓርቲ ደረጃ መደራጀትና መወዳደር ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ አገራችንን በአዲስ የፖለቲካ አደረጃጀት ለማዋቀርና፣ የፓርቲ ጽንሰ-ሃሳብ ትርጉም በጭንቅላት ውስጥ እንዲቀረጽ ለማድረግ የግዴታ የፖለቲካ ሬናሳንስ ያስፈልጋል። ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ወሳኝ ናቸው። ይህንን ሆነ ወይም ያኛውን ስም በመለጠፍ ድርጅት ነን ብለው በአዲስ አበባ ብቻ ተወስነው የሚንቀሳቀሱ እየተነሱ የሚፈነጩበትና አገራችንም የውጭ ኃይሎች መጨፈሪያ የመሆኑ ጊዜ ማብቃት አለበት። እንደፓኪስታንና እንደሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የአስተዳደር ችግር እንዳይፈጠር ከተፈለገ በግልጽ ከመወያየት ሌላ አማራጭ ነገር የለም። ስለሆነም አዲስ የክርክርና የውይይት ባህል እንዲሁም ግልጽነት እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። ይህንን ዐይነቱን ክርክርና ውይይት ላለመጋፈጥ ለመሸሸ የሚሞክር ካለ የራሱ የሆነ የተደበቀ ዓላማ አለው ማለት ነው።

የህብረ-ብሄር የመንግስት (Nation-State) ጉዳይ!

እንደሌሎችም ጉዳዮች የህብረ-ብሄር ጉዳይ አስፈላጊነት የሚያከራክርና ኢትዮጵያንም እንደ አገርና እንደ ህብረተሰብ ያለመውሰድና አምኖ ያለመቀበል አዝማሚያ ይታያል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ኢትዮጵያን ገነጣጥለው የየራሳቸውን ትናንሽ መንግስታት ቢመሰርቱ ደስታውን አይችሉትም። በእኛም ለህብረ-ብሄርና ለአንድ ኢትዮጵያ እንታገላለን በምንለው ዘንድ ጽንሰ-ሃሳቡ በግልጽ የተቀመጠና እንድንወያይበት የተደረገ አይደለም።

የህብረ-ብሄር ምስረታ የታሪክ ግዴታ ነው። በተለያዩ አገሮች የተለያየ ሂደት ቢወስድምና፣ ህብረ-ብሄሮች ቢመሰረቱም በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቻ ነው የተጠናቀቀ ህብረ-ብሄር ሊዋቀር የቻለው። የአውሮፓ አገሮች እንደ አንድ ወጥ መንግስት ከመቋቋማቸው በፊት በአንድ አገር ውስጥ ትናንሽ መንግስታት እንደነበሩና ሰፋ ላለ የገበያ ኢኮኖሚና ለህብረተሰብ አወቃቀር አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ግልጽ ነው። ለምሳሌ ጀርመንን ብንወስድ እ.እ እስከ 1871 ዓ.ም ድረስ ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ የመሳፍንት አገዛዞች እንደነበሩ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላ ለመሄድ የጉምሩክ ቀረጥ መክፈል የግዴታ ነበር። ጀርመንም እንደ አገርና እንደህብረ-ብሄር ያልተዋቀረች ስለነበረች በተለያዩ የወጭ ወራሪዎች፣ በስዊድን፣ በዴንማርክ፣ በፈረንሳይና በአውስትሪያ በተደጋጋሚ ስትጠቃ ነበር። በሌላ ወገን ግን የተለያዩት የመሳፍንት አገዛዝ በየራሳቸው ክልል ውስጥ ትናንሽ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችና ሰፋ ብሎ የተዘረጋ አስተዳደር ነበራቸው። በደንብ የተዋቀሩም የማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ከተማዎች ነበሯቸው። የስራ-ክፍፍልም ይታይ ነበር።  ይህ ሁኔታና በኋላ ላይ የፕረሺያ አገዛዝ ተጠናክሮ መውጣትና፣ አልፎም አንዳንዶችን በጦር ኃይል በቁጥጥር ስር ማዋል ለጀርመን አንድ ወጥ መንግስት በ1871 ዓ.ም መመስረት መንገዱን አዘጋጀ። በዚህም ምክንያት የህብረ-ብሄር መንግስት የሚለው አስተሳሰብ እንዲቀረጽና ይህንን ሊያሰተሳስር የሚችል ሰፋ ያለ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ አስፈላጊ ሆነ። ቀስ በቀስም የውስጥ ገበያ ሲዳብርና በአንድ ገንዘብ አማካይነት የንግድ ልውውጥ ሲዳብርና የባቡር ሃዲድ ሲዘረጋ የከበርቴው መደብ የበላይነቱን ተቀዳጀ። አገር፣ ህብረ-ብሄርና ባንዲራ፣ እንዲህም ህዝብ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ተቀባይነትን አገኙ። ስለሆነም የጀርመንም ሆነ የእንግሊዝ ወይም የፈረንሳይ ህዝብ በየአገሮቻቸው እንደ አንድ ህዝብ የሚቆጠሩ እንጂ፣ እንደ አገራችን የኦሮሞ ህዝብ፣ የአማራና የትግሬ ወይም የሌላ ህዝብ እየተባለ አይደለም የሚጠራው። ይህ ዐይነቱም አባባል ሳይንሳዊ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ብሄር ወይም ብሄረ-ሰብ እንደ አንድ ህዝብ የሚታወቀውና የሚጠራው ለአንድ ህብረተሰብ መኖርና መንቀሳቀስ የሚያስችሉትን፣ ፓለቲካዊ፣ ርዕዮተ-ዓለማዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ስነ-ምግባራዊ፣ እንዲህም የራሱ የሆነ የመነጋገሪያ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የመጻፊያም ቋንቋና ሌሎች ሌሎች ነገሮችን አሟልቶ ሲገኝ ብቻ እንደ አንድ ህዝብ ሊቆጠር ይችላል። በተጨማሪም በስራ-ክፍፍል የዳበረ ከሆነና የራሱ የሆነ ቢሮክራሲያዊ አወቃቀር ካለው እንደ አንድ ህዝብ ሊቆጠር ይችላል። ይሁንና ወደ ህብረተሰብ ሳይንስ ወይም ሶስዮሎጂ ስንመጣ በአንድ አገር ውስጥ አንድ ህዝብ አለ ብሎ መናገር ቢቻልም ሁሉም አንድ ዐይነት ስነ-ልቦናዊና ያለውና በአንድ ዐይነት ሙያ የሰለጠነ አይደለም። በሌላ አነጋገር በገቢ ደረጃ ወይም በመደብ የተከፋፈለ ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ በራሱ ብሄረሰብ የሚለውን ውስን አስተሳሰብ የሚቃረን ነው። ስለሆነም በሳይንስ ስሌት ብሄረሰብ የሚለው አባባል ቦታው አይኖረውም ማለት ነው። አንድን ብሄረሰብ ብሄረሰብ ተብሎ የሚያስጠራው በራሱ የስራ-ክፍፍል ከሌላና ከሌላው ጋር የማይገናኝና ተዘግቶ የሚኖር ከሆነ ብቻ ነው። እንደዚህ ዐይነቱን አደረጃጀት ደግሞ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል። ግሎባል ካፒታሊዝም ሁሉንም አገሮች አመሰቃቅሎአቸዋል። ከክልል ውጭ ወጥተው እንዲንቀሳቀሱ አስገድዷቸዋል። በሌላ ወገን ከዕውቀት ማነስ የተነሳ የማንነት መለያ የሚለውን አንጠልጥለው በመዞር በቅዠት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል።

ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ በአገራችን ውስጥ የህብረ-ብሄርን ጽንሰ-ሃሳብ ለማስረገጥና፣ ብሄራዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የተፈጠረው ችግር በየብሄረ-ሰቡ ውስጥ ከበርቴያዊ አስተሳሰብ መዳብር ባለመቻሉ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የብዙዎቹ ብሄረ-ሰብ ኢኮኖሚዎች አወቃቀር፣ በከብት እርባታ፣ በግብርናና በዘላንነት ወይም በአዳኝነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። በየብሄረ-ሰቡ ውስጥ በጎጆ ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ምርታዊ ክንውን ባለመኖሩና የስራ-ክፍፍሉም የዳበረ ስላልነበር የውስጥ ገበያን ማዳበር አልተቻለም ነበር። በአስተዳደርም ደረጃ የተዋቀረ ቢሮክራሲያው ነክ አደረጃጀት አልነበረም። በዚህ መልክ ተዝረክርኮ የተዋቀረው ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ለሌሎች ባህላዊ ዕድገቶችና እንቅስቃሴዎች፣ ለምሳሌ ለሊትሬቸር፣ ለሙዚቃ፣ ለፍልስፍና ለአርኪቴክቸርና ለልዩ ልዩ ህብረተሰቡን ሊያስተሳስሩ ለሚችሉ ነገሮች መዳበር አመቺ አልነበረም። ይሁንና ግን የኢትዮጵያን የንጉሳዊ ታሪክ ባህል ስንመለከት ወደ ህብረ-ብሄረሰብም የማምራት አዝማሚያና ህዝቡን ሊያገናኘው የሚችል ባህላዊ ምልክቶች ነበሩ፤ አሉም።

የኢትዮጵያን ታሪክና የህብረተሰብ አወቃቀር አስቸጋሪና በጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ፣ የህብረ-ብሄር ምስረታ ከኢምፔሪያሊዝም አይሎ መውጣት ጋር መጋጨቱና፣ ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ግንባታ መዘርጋት ያለመቻሉ ነው። በ19ኛ ክፍለ-ዘመን አይሎ የወጣው ኢምፔሪያሊዝም እንደሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማጨናገፍ ጀመረ። ለኢንዱስትሪ ምስረታና ለውስጥ ገበያ መዳበር እንቅፋት ሆነ። እንደ ጃፓን የሚጄ ዲይናስቲ ዐይነት ቆራጥ አገዛዝ ባለመፈጠሩ ኢትዮጵያ ለኢምፔሪያሊዝም መጨፈሪያ መድረክ ሆነች። ሃሳቡ የተጋጨበትና የሚጋጭበት፣ የማንነት ቀውስ የተዋሃደው የህብረተሰብ ክፍል ብቅ አለ። በዚህም ምክንያት ከየብሄረ-ሰቡ የወጣው ኤሊት ነኝ ባይ ብቻ ሳይሆን ራሱ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ የሚለው የአገር-ወዳድነት ስሜት ችግር ተፈጠረበት። ይህንን በሚገባ ለመረዳት ዘርዘር አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው ሁኔታ የባሰውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አዘበራረቀው። ግልጽ የውስጥ ገበያ ማዳበር አለተቻልም። ከበርቲያዊ መደብም መፍጠር አልተቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የተዝረከረከው ኢኮኖሚ ብሄራዊ ንቃተ-ህሊናን ሊያዳብር የሚያስችልና እንደ አንድ ህዝብ እንድንነሳ የሚያደርገን አልነበረም። በተለይም በ1950ኛው ዓመተ ምህረት መጀመሪያና ከዚያ በኋላ ተግባራዊ መደረግ የነበረበት ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ተቋምን ማዋቀርና ህብረተሰቡን ማያያዝ፣ ብሄራዊ ባህይርና ብሄርተኝነት እንዲፈጠር ከአዲስ አበባ ውጭ ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ለምሳሌ እንደ ቲያትር ቢቶችና ሌሎችንም ማስፋፋትና ማዳበር ሲገባ፣ አገዛዙ ሆን ብሎ የያዘው አትኩሮውን በአዲስ አበባ ብቻ መወሰን ነበር። ፍሪድርሽ ሺለር እንደሚለን አንድ አገር እንደ ህብረ-ብሄር እንድትዋቀርና እንድትገነባ ከተፈለገ ከኢኮኖሚና ከከተማዎች ግንባታ ባሻገር ብሄራዊ ባህርይ ያለው የድራማና የቲአትር መድረክ በአገር ውስጥ ማስፋፋት ያስፈልጋል ይላል። ይህ ዐይነቱ አስፈላጊ ጉዳይ ተግባራዊ ሊሆን ባለመቻሉ የግዴታ የፊዩዳላዊ የማፍንገጥና የማኩረፍ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። ስለሆነም መጠናቀቅ ያለባቸው ህብረ-ብሄራዊ የግንባታ መሰረተ-ሃሳቦች ለአፈንጋጭ ኃይሎች ሁኔታውን አመቻችቶ ሰጣቸው። የዚህም ሆነ የዚያ ተጠሪ ነን፣ ለነፃነት እንታገላለን የሚሉ በእርግጥ ደግሞ የነፃነትን ትርጉም ያልተገነዘቡ የብሄረ-ሰብ አንቅስቃሴዎች ብቅ አሉ። በሰላምና በውይይት፣ እንዲሁም በክርክርና በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና ለአንድ ዓላማ ለመታገል ሰፊ መድረክ እንዳይፈጠር መንገዱን ዘጉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ አርቆ-አሳቢነት ወደጎደለው ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሲያማራን፣ በዚያው መጠንም ኃይልን አስተባብሮ አንድ ዲሞክራሲያዊና ሪፑብሊካዊ እንዲሁም ጠንካራ አገር እንዳንመሰርት አገደን። ከፍተኛ የሆነ የሰውና የማቴሪያል እንዲሁም የገንዘብ ኃይል ወደመ። ለዚህ ዐይነቱ የህብረ-ብሄር ግንባታ ዕንቅፋትም ሌላው ምክንያት ራሱ አገዛዙ በኤምፔሪያሊዝም ጉያ ስር መውደቁ ነው። ወታደሩ፣ የስለላ መዋቅሩና ፖሊሱ ሁሉ በውጭ ኃይሎች የተገነቡ ስለነበር ከውስጥ ሆኖ ለማመስ ቀላል ነበር። የሲቪል ቢሮክራሲውም አስተሳሰብ ብሄራዊ ንቃተ-ህሊና የጎደለው ስለነበር ለአገር ግንባታ አስተዋፅዖ ሊያደርግ አልቻለም። እንዲያውም እንቅፋት በመሆን ከውስጥ ብሄራዊ ነፃነታችን እንዲቦረቦር አደረገ።

ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት የተዋቀረው የክልል አገዛዝ ሁኔታውን አባባሰው። የህዝቡን አመለካከት አዘበራረቀው። ኢኮኖሚውን በዘረፋ ላይ እንዲካሄድ አደረገው። ከተማዎች ወደመንደርነት እንዲለወጡ አደረገ። ባጭሩ ለጠንካራ አገር መገንባት መሰናክሎች ፈጠረ። በዚህ ዐይነት የተዝረከረከ ህብረተሰብና የኢኮኖሚ አወቃቀር እንዴት ተደርጎ አገርን መገንባት ይቻላል? እንዴትስ ብሄራዊ ስሜትን ማዳብር ይቻላል? በሚለው ላይ በሰፊውና ብግልጽ መነጋገር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የውጭ ኃይሎችንም አሻጥር በግልጽ መነጋገርና ድርጊታቸውንም ገደብ እንዲኖረው  ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የእኛ ንቃተ-ህሊንና የምሁር ኃያልነት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የእኛ በአንድነትና ለአንድ ዓላማ መቆማችን ወሳኝ ነው። ለማንም የውጭ ኃይል ቀዳዳ የማንሰጥና ዕውነተኛ ብሄረተኝነት የተላበስን መሆን አለብን። በተጨማሪም በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ ኃይልና ኃያልነት መኖር አስፈላጊ ነው። አገራችን የኢምፔሪያሊስቶች፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፐሪያሊዝም መጨፈሪያ እንዳትሆን በትጋት መስራት ያስፈልጋል። የሚያሳዝነው ነገር ለዚህ ዐይነቱ ግልጽ ውይይት ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ዝግጁ አለመሆኑ ነው። እንዲያውም አንዳንዱ ዕድሉንና የስልጣን መያዙን ጉዳይ ከአሜሪካን ጋር ያገናኘ ነው የሚመስለው። በዚህም በዚያም ብሎ ይህ ነገር እንዲነሳበት አይፈልግም። ድሮም ሆነ ዛሬ በደፈናው ለብሄረ-ሰቤ ነፃነት እንታገላለን የሚለውን ብቻ ፀረ-ኢትዮጵያና የአንድነት ፀር አድርጎ መወሰድ አይቻልም፤ ትክክልም አይደለም። ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘት በብሄር አቀፍ ደረጃ ተደራጀሁም የሚለው ተጠያቂ ነው። ድሮም ሆነ ዛሬም አቋሙ ግልጽ አይደለም። በእየአንዳንዱ ነጥብ ላይ ግልጽ አቋም ከሌለንና ለማስረዳት ካልቻልን፣ ከዚህም ባሻገር የውስጥ ለውስጥ አሻጥር የምንሰራና መሰናክል የምንፈጥር ከሆነ እንዴት አድርገን ነው ለብሄራዊ አንድነት መታገል የምንችለው። በአንዳንዶቻቸን ዘንድ አሁንም ቢሆን የድሮው የተማሪው ዐይነት እንቅስቃሴ ሁኔታ ነው እንጂ የሚታየው ከበርቴያዊና ምሁራዊ አስተሳሰብ ማዳበር በፍጹም አልቻልንም። ቶሎ ብለን ወደኩርፊያና ወደ መሻኮት እናመራለን። ቡድናዊ ስሜት እናዳብራለን። በሃሳብና በምሁራዊ ውይይት ዙሪያ ሰውን ለመሰብሰብ ከመሞከር ይልቅ አግበስብሰን ተከታዮችን ለማፍራት እንሽቀዳደማለን። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ የመሽሎክለክ ጨዋታና ሽወዳ እስካልተላቀቅን ድረስ አስር ጊዜ ኢትዮጵዊ ነን፣ ኢትዮጵያችንም ዘለዓለም ትኑር እያልን ብንጮህ ትግሉን ከማጨናገፍ በስተቀር ሌላ የምንሰራው ቁም ነገር የለም።

ለብሄረሰብ ነፃነታችን እንታገላለን የምትሉ ደግሞ በጠቅላላቅው ያለንን ደካማና አስቸጋሪ ሁኔታ በመገንዘብ ሰፋ ላለ ምሁራዊ ውይይት መዘጋጀት አለባችሁ። ከመገንጠል ሌላ አመራጭ የለንም፣ ብሄረ-መንግስት ነበረን፣ እሱን መልሰን መቀዳጀት አለብን እያላችሁ ወደማይደረስ ህልም የሚደረገው ምሁራዊነት የጎደለው ትግል የመጨረሻ መጨረሻ ሁላችንንም ያጠፋናል። እያንዳንዱ ግለሰብ ምኞቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚችለውና የሚመኘውን ማግኘት የሚቸለው በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ምን ዐይነት ፊዴራላዊ አወቃቀርና የሪፑብሊክ አመሰራረት ነው የሚያዋጣው በሚለው ላይ  መነጋገር ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ግን በቁጥር የምንበልጥ አኛ ነን፣ ስልጣን የሚገባን ለኛ ነው የሚለው አነጋገርና መመጻደቅ አደገኛ አካሄድ ነው። በቁጥር በልጦ መገኘት ሳይሆን ዋናው ቁም ነገር ጥራት ያለው ግልጽ የሆነ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ትግል ነው ወሳኝነት የሚኖረው። ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ በሳይንሱ ማሳየት ነው። ያም ሆነ ይህ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ መከፋፋል አይቻልም። ወያኔም ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት ሞክሮ ሞክሮ አልተሳካለትም። ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምኞቱንና ፍላጎቱን አንድ ላይ ብቻ ሆኖ ዕውን እንደሚያደርግ ከምንጊዜውም በላይ ተገንዝቧል። ይህንን የህዝብ ፍላጎትና ስሜት መቀበል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያውነቱን እንዲሽር መግትጎትና በብሄረ-ሰቡ ብቻ ዕምነት እንዲኖረውና እንደርዕዮተ-ዓለም እንዲቀበለው የሚደረገው አጉል ቅስቀሳ የታሪክ ወንጀል መስራት ነው። ወደ ጭፍንነትና ወደ እርስበርስ ጦርነት የሚያመራ ነው። የሰውን ልጅ ታሪካዊ ተልዕኮ የሚፃረር ነው። ስለዚህም ግለሰብአዊ ነፃነትና በብሄር ግንባር የማይወከል ህዝባዊ መብት የሚከበርበትን አገር የመፍጠሩ ጉዳይ ወሳኝ ይሆናሉ። ለዚህ ደግሞ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ድህነትንና ረሃብን አስወግዶ ጠንካራ የሆነ ብሄረ-አቀፍ ኢኮኖሚ መገንባት ነው። በብሄረ-ሰብ ደረጃ ተደራጀን የሚሉ በመሰረቱ የየብሄረ-ሰቦቻቸውንና የግለሰቦችን መብት ማስጠብቅና ማስከበር አይችሉም። በታሪክ እንደታየው ተጠቃሚው ኤሊቱ እንጂ ሰፊው ብሄረ-ሰብ አይደለም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና አካሄድ ለንዑስ ከበርቴው ፋሺሽታዊ መሰረት ይጥልለታል። ከግላዊ ነፃነትና አገራዊ ብልጽግና ይልቅ ድህነትና ድንቁርና ይስፋፋሉ። ይህ በራሱ አገርን ለውጭ ጠላት አጋፍጦ ያሰጣል። የተዳከመና የተበታተነ አስተሳሰብ ያለው ህዝብ ለውጭ ወራሪዎች አመቺ ነው።፡

ሌላው በግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ ልዩ ልዩ ነገሮችና አንድነት ተያይዘው የሚሄዱና የተፈጥሮ ህግም ናቸው። እንደሚታወቀው የሁሉም ነገር ምንጭ አንድ ነገር ብቻ ነው። ከዚያ አንድ ነገር በመነሳት ነው ሌሎች ነገሮች እየተለያዩና እየተሰበጣጠሩ የመጡትና የሚመጡት። ይሁንና ግን እነዚህ የተለያዩ ነገሮች(diversified) እዚያው በዚያው በአንድነት የሚኖሩ እንጂ እንደጠላት ተለያይተው የሚኖሩ አይደሉም። ተፈጥሮ በተለያዩ አፅዋዕትና እንስሳት ሁሉ የምትገለጽ እንደመሆኗ መጠን፣ በዚህም አማካይነት ብቻ የተለያዩ አፅዋዕትና እንስሳት በተፈጥሮ ውስጥ የሚደርስባቸውን ጥቃት መቋቋም ይችላሉ። በተጨማሪም የተለያዩ ነገሮች በአንድ ላይ መኖር እንደውበት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ አንድ ብሄረ-ሰብ ራሴን ገንጥዬ ልውጣ ቢል ሊያድግ አይችልም፤ የሚመኘውንም ነገር ሊያገኝ አይችልም። በአንድ ወጥ አስተሳሰብ ብቻ ስለሚዋጥ አዳዲስ ነገሮችን ሊፈጥር ወይም ከሌላው ሊማር አይችልም። የሰውን ልጅ ታሪክ ስንመለከት አንዱ ከሌላው በመጋባትና በመዋለድ የማሰብ አድማሱን እያሰፈና አዳዲስ የአኗኗር ስልት እያዳበረ ነው እዚህ ደረጃ ለመድረስ የበቃው። በመሆኑም አንዳንድ ኤሊት ነን ባዮች የሚያነሱት፣ „ይህ የኔ ብቻ ነው“፣ „አትድረሱብኝ“፣ „በክልሌ ተወስኜ መኖር እፈልጋለሁ“  የሚለው አባባል የመጨረሻ መጨራሻ ራሱ ተገንጣዩን ነው የሚጎዳው።

ከዚህ ስንነሳ ያለን አማራጭ አንድ ነገር ብቻ ነው። ኃይልን አሰባስቦ ታላቅና የተከበረች አገር መገንባት። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባላቤት መሆን። ትላንትናና ዛሬም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ትግል በዚህ ላይ ነው። ሁሉም በአንድ አገር የሚገኝ የብሄረ-ሰብ ኃይል በየፊናው እታገላለሁ የሚል ከሆነ የግዴታ ለውጭ ኃይሎች መሳሪያ ነው የሚሆነው። የተዳከመና የተሰበጣጠረ ኃይል ለውጭ ኃይሎች ማመስ ያመቻል። ስለዚህም አንዳንድ ኃያላን መንግስታት ከጎናቸን ይቆማሉ ብሎ ማመን የዋህነት ነው። ይህንን ወይም ያኛውን ተንቀሳቃሽ ኃይል የሚደግፉት ለመበጥበጥ እንዲሚያመቻቸው በማመን እንጂ የአንድን ብሄረ-ሰብ ነፃነት በመሻት አይደለም።

ከዚህ ባሻገር በተለይም ለአንድ ኢትዮጵያና ብሄራዊ ነፃነት እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ዕድላቸውንና ዕምነታቸውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ማገናኘት አለባቸው። በአንዳንዶች የሚነፍሰው ከአሜሪካ ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አንችልም የሚለው አስተሳሰብና ቅስቀሳ ከሳይንስ ውጭና ታሪከ-ቢስ አባባል ነው። የአንድ አገር ዕድል ሊወሰን የሚችለው በዚያው በአገሩ ህዝብና በአገሩ የምሁር ኃይል ብቻ ነው። አስር ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝን ኃይል ዘመዴ ነው፣ ከጎኔም የቆመ ነው እያሉ መጥራት፣ እባክህን አገሬን የጦር አውድማ አድርግልኝ ብሎ እንደመጋበዝ ይቆጠራል። ወደ ስልጣኔና ወደ ህብረ-ብሄር ግንባታ የሚያመራው ትክክለኛው መንገድ አይደለም። ስለዚህም በራሳችንና በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ዕምነት እንዲኖረን ያስፈልጋል።

የኢኮኖሚ ጥያቄና አፈታት ችግር ጉዳይ!

በማንኛውም አገር ውስጥ ከፖለቲካና ከዲሞክራሲ ባሻገር የኢኮኖሚ ጥያቄ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ፖለቲካና ዲሞክራሲ ጣራና ግድግዳ ሲሆኑ፣ ኢኮኖሚ መሰረት ነው። በአሸዋ ላይ የተገነባ ቤት ዘላቂነት የሌለውን ያህል፣ በፀና የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ያልተገነባ አገር ሁልጊዜ በውዝግብ ዓለም ይኖራል። ስለዚህም ለአንድ አገር ዘላቂነትና ተቻችሎ መኖር የግዴታ የኢኮኖሚ ጥያቄ ቁልፍ ቦታን ይይዛል።

በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የኢኮኖሚን መሰረታዊ ቦታ በቅጡ አለመረዳት ነው። ይህ ችግር የተፈጠረውና የሚፈጠረው አብዛኛዎች የአፍሪካ መንግስታት፣ ኢትዮጵያንም ጨምሮ ስለሰው ልጅ ያላቸው ግንዛቤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተጨማሪም ስለ አገርና ስለ ህብረተሰብ ምንነት ትርጉም የተረዱ አይመስሉም። በመሆኑም አንድ አገር እንዴት ደረጃ በደረጃ መገንባትና ህብረተሰቡ እርስበርሱ መያያዝ እንዳለበት እንደመሰረታዊ ጉዳይ የተወሰደ አይደለም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታት፣ ኢትዮጵያንም ጨምሮ የህዝቦቻቸው አልኝታ ሳይሆኑ የወጭ ተላላኪና በሪሞርኪ የሚጠመዘዙ ነው የሚመስለው እንጂ ታሪክን ለመስራት የተኮተኮቱ አይደሉም።  በዚህም ምክንያት የአፍሪካ መንግስታት ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር እጅና ጓንቲ በመሆን የአህጉሪቱን ሀብት እየዘረፉና ህዝቡን እያደኸዩት ነው።

በመሆኑም የአፍሪካ መንግስታቱም ሆነ ኢሊቱ ስለኢኮኖሚ ትርጉም ያላቸው ግንዛቤ እጅግ ደካማ ነው። አብዛኛዎቻችን በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ በሚክሮና በማክሮ ኢኮኖሚክስ የሰለጠን በመሆናችን በአንድ አገር ውስጥ እንዴት ህብረተሰብአዊ ሀብት ተፈጥሮ በስነስርዓት ለህዝቡ እንደየአስተዋፅዖውና እንደየደረጃው እንደሚከፋፈል ግልጽ በሆነ መልክ የተረዳን አይደለንም። የማክሮና የሚክሮ ኢኮኖሚክስ መጽሀፎችን ላገላበጠ ስለአገርና ስለህብረተሰብ ግንባታ የሚያወሩት ነገር ምንም የለም። ካፒታሊዝም መቼ እንደተጀመረ፣ ለምንስ በተወሰነ አካባቢ ብቻ ማደግና መስፋፋት እንደቻለ፣ በምንስ ውስጣዊ ህጎች እንደሚሰራ አያስረዱም። በማክሮ ኢኮኖሚና በሚክሮ ኢኮኖሚ አመለካከት ሁሉም ነገር ያለና የተሰጠ(given) ስለሆነ የህብረተሰብን ዕድገት ደረጃ በደረጃ አያሰቀምጥም። ከዚህም በላይ ለምሳሌ ምርትን ለማመረት የሚያገለግሉ ነገሮች ወይም ሪሶርስ በተቆጠበ(Scarce) መልክ እንደሚገኙ ሲያወሳ፣ በተለይም ካፒታል  በሶስተኛው ዓለም አገሮች በብዛት አይገኝም ይለናል። ስለዚህም ይላል፣ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ካፒታል በብዛት ከሚገኝባቸው ከኢንዱስትሪ አገሮች ማስመጣት እለባቸው። እዚህ ላይ ካፒታል ሲል የገንዘብ ወይስ የፊዚካል መሆኑን ግልጽ ባይሆንም፣ ሁለቱንም ብንወስድ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይልና የዕውቀት፣ እንዲሁም የዕድገት ደረጃ ውጤቶች ናቸው። የሁሉንም የካፒታሊስት አገሮችን መነሻ ስንመለከት ከምንም ተነስተው ነው የተወሳሰበና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት የቻሉት። በሌላ አነጋገር ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር አልተፈጠሩም። ወይም አምላክ ለእነሱ ብቻ ከላይ አልወረወላቸውም። በግለሰቦች ጥረትና በሙከራና በልምድ ነው ሳይንስና ቴክኖሎጂዎ ሊፈጠሩና ተግባራዊም ሊሆኑ የቻሉት። ስለሆነም ከተፈለገና ታታሪነት ካለ በተለይም የፊዚካል ካፒታልን መፍጠርና ማሳደግ ይቻላል። የገንዘብ ካፒታል ደግሞ ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር የሚሄድና ጥንካሬም የሚያገኝ ነው። የአንድ አገር ዕድገት በዶላርና በሌላ የውጭ ካረንሲ የሚወሰን ሊሆን አይችልም። የዶላርና የኦይሮ ሞኖፖሊ ብዙዎችን ኤክስፐርቶችን እያነጋገረና በጥያቄ ውስጥም እየተቀመጠ የመጣ ነው። ስለሆነም የውጭ ካረንሲን እንደ አንዱ የምርት ኃይል አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው። በተለይም ፕሮፌሰር ሶዲ እንደሚያስተምሩን፣ ታታሪነትንና የማሰብ ኃይል፣ ኃይልና(Energy) ማሽን ናቸው እንደ ሀብት መፍጠሪያና ማዳበርያ ዘዴ መወሰድ ያለባቸውና ትክክለኛውም መንገድ። በዚህም ምክንያት ማክሮና ሚክሮ ኢኮኖሚክስ ስለሀብት ዋናው ምንጭ፣ ማዳባሪያ ዘዴ፣ ስለሀብት ዕድገትና ክፍፍል ብዙም የሚነገሩን ነገር የለም። በጂዲፒ የሚገለጸው የኢኮኖሚ ዕድገት ስለ-ስራ ክፍፍል አስፈላጊነትና መዳበር፣ እንዲሁም ስለ ሳይንስና ስለቴክኖሎጂ፣ በተጨማሪም ስለከተማዎች ዕድገትና በልዩ ልዩ ነገሮች መተሳሰር የሚያወራው ምንም ነገር የለም።

ከዚህም በመነሳት የአንድ አገር የኢኮኖሚ ችግር በነፃ ገበያ አማካይነት በአቅራቢና በጠያቂ መሀከል ሊፈታ ይችላል የሚለው በቁንጽል መልክ የቀረበው አስተሳሰብ ለጤናማ የኢኮኖሚ ውይይትና አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብናል። እንደሚታወቀው የኢኮኖሚክስ ዕውቀት እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ፊዚክስ፣ ኪሜስትሪና ባይሎጂ የመሳሰሉት፣ ተፈጥሮን በመመልከትና በመመርመር፣ አንዲሁም በማጥናት የተደረሰበትና የሚደረስበት ዕውቀት ሳይሆን፣ የአንድን ህብረተሰብ የአወቃቀር ስርዓት በመመልከት የዳባረ ነው። አንድን ህብረተሰብ ለማጥናት፣ በምን ነገሮች ላይ ቆሞ ነው የሚንቀሳቀሰው፣ የስራ ባህሉስ ምንድነው ለሚለው በምዕራቡ የፍልስፍናና የህብረተሰብ ሳይንስ ዘንድ በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ የተለያዩ የአተናተን ዘዴዎች አሉ። የተለያየ አመለካከትና የፍልስፍና መሰረት ያላቸው የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ህብረተሰብአቸውን በተለያየ መነጽር ነው የሚመለከቱት። በዚህም የተነሳ በተለይም ኢኮኖሚክስ በከፍተኛ ደረጃ በርዕዮተ-ዓለም የተወጠረና የታጠረ በመሆኑ የትኛው ነው ትክክለኛው ለሚለው ከፍተኛ መፈላጥ እየተካሄደ ነው። አንድ በእርግጥ ማለት የሚቻለው ነገር፣ የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል አመለካከት ለጊዜው በአሸናፊነት በመውጣት ህብረተሰቦችን እያተረማመሰ ነው። የኒዎ-ክላሲካል መተንተኛም ዘዴ የአንድን ህብረተሰብ ውስጣዊ ህጎችና የዕድገት ደረጃዎችና፣ በልዩ ልዩ መስኮችና የህብረተሰብ ክፍሎች መሀከል ያለውን መተሳሰረና ጥገኝነት በመውሰድ ሳይሆን ሞዴል ለማውጣት የሚሞክረው በክስተት(Phenomenon) ላይ ብቻ በመመርኮዝ ነው። እኛም ሳናውቀው የዚህ ርዕዮተ-ዓለም ሰለባ በመሆን ግራ ተጋብተናል። እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ሌሎች ግልጽና ለህብረተሰብ ግንባታ የሚያገለግሉ ግሩም ግሩም የኢኮኖሚክስና የዕድገት መጽሀፎችና ዕውቀቶች እያሉ አብዛኛዎቻችን ለምን ጭንቅላታችን ለተቀደሰው ነገር እንደተጋረደ በፍጽም አይገባኝም። ልክ እንደ ሃይማኖት ወይም እንደኮሙኒስት ርዕዮተ-ዓለም አንድ አመለካከት ብቻ ይዘን ወደፊት መሸምጠጡ ለዕውነተኛ ምሁራዊ ክርክር ዕንቅፋት ሆኗል ማለት እችላለሁ።

ያም ሆነ ይህ ከእነ አዳም ስሚዝ በኋላ የፈለቀው የገበያ ኢኮኖሚ ትምህርትና አስተሳሰብ እያንዳንዱን ህብረተሰብ በተናጠል ወስዶ መመልከት፣ መመርመርና ማጥናት ሳይሆን አንድ ለሁሉም አገሮች ሊያገለግል የሚችል ዓለም አቀፋዊ ህግ አለ ወደሚለው ተቀባይነት ወዳገኘ ዶግማ ውስጥ ከቶናል። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና ዕምነት ደግሞ ልክ የካቶሊክ ሃይማኖት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ 15ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የአውሮፓን ህዝብ ጭንቅላት ወጥሮ በጨለማ ውስጥ እንዲኖር እንዳስገደደው ሁሉ፣ የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል አመለካከት በመስፋፋቱ ብዙ የሶስተኛው ዓለም ህዝቦች በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። በጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደማይችል የእግዚአብሄር ቃል አድርገው አምነው ተቀብለውታል። ዕውነትን ከውሸት እንዳይለዩ መንገዱ ሁሉ ጠፍቶባቸዋል።  ስለዚህም አገሮች በሙሉ ካሉቡትና ከሚኖሩበት ተጨባጭ ሁኔታ ባሻገር ይህንን በምዕራቡ ዓለም የተወሰነ አመለካከት ባላቸው የኢኮኖሚክስ አዋቂ ነን በሚሉ የዳባረውን ከሳይንስ ውጭ የሆነውን የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንዲቀበሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገደዋል።

የኢኮኖሚክስን ዕውቀት በሚመለከት ከጥንቱ የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ውይይት የተደረገበት ነው። ኢኮኖሚክስ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የመነጨው ቤተሰብን ማስተዳደር(House Hold Management) ከሚለው ነው። ይሁንና ፕላቶን በሪፑብሊክ መጽሀፉ ውስጥ ስለ ስራ-ክፍፍልና ስለንግድ አስፈላጊነት አስፍሯል። የስራክ-ፍፍልም መኖር የግዴታ አንድን ህብረተሰብ እንደሚያቀራርብና አስፈላጊም እንደሆነ ያወሳል። ይህም ማለት ከንግድ በፊት የሰራ-ክፍፍልና ምርት መቅደም አለባቸው። ሲመረት ብቻ ነው የገበያ ልውውጥ ሊኖር የሚችለው። ለማምረት ደግሞ የግዴታ የምርት መሳሪያዎች መኖር አለባቸው። ይህ ሁኔታ በሌለበት አገር ውስጥ ስለምርትና ስለንግድ ልውውጥ ማውራት አይቻልም። ይሁንና ደግሞ ስለኢኮኖሚ በሚወራበት ጊዜ እንዲያው ለማምረት ተብሎ የሚመረት ጉዳይ አይደለም። ኢኮኖሚ የሚገለጸው የሰው ልጁ ከተፈጥሮ ጋር በሚያደርገው ግኑኝነት፣ በማሰብ ኃይሉ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች አይ እያወጣ ቅርጽና መልክ እየሰጠ ይጠቀማል፣ የእርሻ ሰብል ደግሞ ከሆነ እየዘራና እያመረተ የራሱን ምንነት ይገልጻል። ስለዚህም የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው በማሰብ ኃይሉ ተፈጥሮን ለራሱ መጠቀሚያ ሲያደርግና፣ በየጊዜው ደግሞ ኑሮውን እያሻሻለ ሲሄድ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ግኑኝነት ሲያደርግና ሲሰራ የማሰብ ኃይሉንና ሰውነቱን በመጠቀም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተፍጥሮን ይለውጣታል፤ ወይም ደግሞ በተፈጥሮ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። በተፈጥሮና በሰው ልጅ መሀከል መደጋገፍ ሲኖር፣ ተፈጥሮ ሳትሆን የሰው ልጅ ለመኖር ሲል ሙሉ በሙሉ የሚመካው በተፈጥሮ ላይ ብቻ ይሆናል። ስለዚህም ኢኮኖሚ ተራ የማምረትና የልውውጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው የሰው አካል እንቅስቃሴና የማሰብ ኃይል የሚገለጽበት፣ የሰው ልጅ ራሱን የሚያሻሽልበትና ከአንድ የዕድገት ደረጃ ወደ ሌላ የሚሸጋገርበት ነው። ኢኮኖሚያዊ ድርጊት ሜታቦሊካል ነው። ይህም ማለት ኢኮኖሚ ሁለንታዊ ነው ማለት ነው።

ከዚህ ስንነሳ የሰው ልጅ እንደ ማሀብረሰብ ሲደረጃና ሲያመርት፣ እንዲሁም ደግሞ የስራ ክፍፍል ሲዳብር የግዴታ መገበያየት አስፈለገ። እንደሚታወቀው ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሁሉንም ማምረት ስለማይችል፣ ሌላው ሌላ ዐይነት ምርት ካመረተው ጋር ልውውጥ ለማድረግ ሲል ገበያ የሚባለው ኢንስቲቱሽን ተፈጠረ። በመጀመሪያው የነበረው የዕቃ በዕቃና የምርት በምርት ልውውጥ በገንዘብ አማካይነት በመተካት ለገበያ ኢኮኖሚ መዳበር ልዩ ዕምርታና ገጽታ ሰጠው። ይሁንና ግን በመጀመሪያው ወቅት የነበረው የገንዘብ ዐይነት አመቺ ስላልነበር፣ በቀላሉ ሊሽከረከር የሚችል ከመዳብ፣ ከብርና ከወርቅ የተሰሩ የገንዘብ መለዋወጫ ዘዴዎች ተፈጠሩ። የገበያ ኢኮኖሚ እየዳበረና እየተወሳሰበ ሲመጣ ወርቅም ሆነ ብር እንደልብ ይገኙ ስላልነበር የገበያ ዕድገትና ንግድ ወደ ሚቀዘቅዝበት ሁኔታ ተፈጠረ። በ17ኛው ከፍለ-ዘመን መጨረሻ ላይ በወርቅ የተደገፈና በወርቅ ሊለወጥ የሚችል የወረቀት ገንዘብ ማተም አስፈላጊ ሆነ። ይህ ዐይነቱን በወርቅ ላይ የተደገፈ የገንዘብ ዐይነት ከ1900 ዓ.ም ጀምሮ አባዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ አገሮች ተግባራዊ በማድረግ ለንግድ ልውውጥና መስፋፋት ይጠቀሙበት ጀመር። ከመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ጀምሮ በወርቅ ዕጥረት የተነሳ በወርቅ ላይ የተደገፈ የገንዘብ ልውውጥ ከቀረ በኋላ እንደገና ደግሞ በ1930ዎቹ ጀምሮ ለጊዜው ተግባራዊ ከሆነና ከፈረሰ በኋላ፣ የመጨረሻ መጨረሻ በ1944 ዓ.ም በብሬተንስ ውድስ ስምምነት አማካይነት በኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ፣ በተለይም የውጭ ገበያን በሚመለከት በወርቅ ላይ የተደገፈ የገንዘብና የንግድ ልውውጥ ተቀባይነትን አገኘ። በ1971 ዓ.ም ይህ ስምምነት በመፍረስ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢንዱስትሪ አገሮች ዋናው መገበያያው ዶላርና ኦይሮ ናቸው። ይህም በዕምነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው እንጂ ከበስተጀርባው በምንም ነገር የተደገፈ አይደለም።

ይህንን የዘረዘርኩት ለምንድነው? በታሪክ ውስጥ በጣም ጥቂት አገሮች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛዎቹ አገሮች እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የገበያን ኢኮኖሚ አዳብረዋል። የስራ-ክፍፍልም ነበራቸው። ይሁንና ግን በሁሉም አገሮች ካፒታሊዝም ሊዳብርና እንደስልተምርት ሊወጣ አልቻለም። በጣም ጥቂት የሆኑ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ በመጀመሪያ እንግሊዝ፣ ቀጥሎ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና አሜሪካ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ጃፓን በመንግስት የተደገፈ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ካፒታሊዝምን ወይም ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ እጀግ የተወሳሰበ የውስጥ ገበያ ማዳበር ችለዋል። ይህንን መንገድ ያልተረዱና ተግባራዊ ማድረግ ያልቻሉ የአፍሪካ አገሮች ወደ ንጹህ የጥሬ-ሀብትና የእርሻ አምራችነት በመለወጥ ወደ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ ማህበረሰብና ህብረተሰብ መመስረት አልቻሉም። በተለይም በትምህርት ቤት ውስጥ የተስፋፋው ዓለም አቀፋዊ የስራ-ክፍፍል የሚለው የኢኮኖሚክስ ትምህርትና፣ በዚህ አማካይነት እያንዳንዱ አገር ቢሰለጥን ኢኮኖሚውን ያሳድጋል፣ ህዝቡም ተጠቃሚም ይሆናል ተብሎ ስለሚሰበክ፣ ብዙዎች ወጣት ተማሪዎች በዚህ የተሳሳተ ዶግማ በመመራት አገሮቻቸውን መቀመቅ ውስጥ መክተት ቻሉ። ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚታየው ድህነትና የኢኮኖሚ መዝረክረክ፣ የከተማዎች በዕቅድ አለመሰራትና ህዝቡ በዘፈቀደ መኖር ከሳይንስ ውጭ የሆነ የኢኮኖሚክስ ትምህርት በመስፋፋቱ ነው።

በዚህ መሰረት ከ1950ዎቹ ጀምሮ በአፍሪካ ምድር የተቋቋሙት የምትክ ኢንዱስትሪ ተከላዎች(Import Substitution Industrialization)  ውጤታማ ያልሆኑት ከተሳሳተ ስሌትና፣ በገበያ ኢኮኖሚ ብቻ ህብረተሰብአዊ ሀብት ይፈጠራል፣ ኢኮኖሚውም ያድጋል ከሚለው ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት በመነሳት ነው። የአውሮፓን የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ በቅጡ ላጠና ግን የገበያ ኢኮኖሚ ቀሰ በቀስ ተግባራዊ መሆን የቻለው በመንግስታት አማካይነት ከተማዎችና መንደሮች ከተነገቡና ህዝቡ መሰባሰብ ከጀመረ ወዲህ ነው። ይህ አዲስ የተፈጠረው ሁኔታ ለዕደ-ጥበብ ስራና ለንግድ ማበብ በሩን ሲከፍት በዚያውም አማካይነት ቀስ በቀስ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ይዳብራል። አዳዲስ የህንፃ አሰራሮችና ስዕሎች፣ ድርማና ኦፔራ በመበልጸግ በአውሮፓ ህዝብ ጭንቅላት ውስጥ ልዩ የማሰብ ኃይል ይዳብራል። እነጋሊሊዪና ኮፐርኒከስ፣ ኬፕለርና ባኮን፣ በኋላም ኒውተንና ጋውስ አንዲሁም ሪማን የዚህ አዲስ የተፈጠረው ሁኔታ ውጤቶች ናቸው። አካባቢዎችና ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ የሰዎች የማሰብ ኃይል በመዳበር የሳይንስ ግኝት መዳበርና መስፋፋት ቻለ። ቀስ በቀስም በሳይንስ አማካይነት ብቻ ካፒታሊዝም ቴክኖሎጂዎችን በማዳበር ዛሬ የምናየውን የበላይነት መጎናፀፍ ቻለ።

ይሁንና ግን ካፒታሊዝም እንደስልተምርት በከፍተኛ ደረጃ ይንቀሳቀስ ዘንድ የግል ሀብት ወሳኝ ሚናን ቢጫወትም፣ በውድድር ዓለም ውስጥ የሚከንፍ፣ በየጊዜው ኢንቬስት ለማድረግ ሪስክ የሚወስድና ትርፍ ለማካበት የሚጣደፍ ከበርቴያዊ የህብረተሰብ ክፍል መኖር አስፈላጊ ነው። ዓላማውም ከአጭር ጊዜ አንፃር የሚነደፍ ሳይሆን፣ ገበያ ውስጥ በተከታታይ ከቆየና የመወዳደርር  ብቃቱን ማሳየት የቻለ እንደሆን ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ትርፍ ያተርፋል። በዚህም መሰረት ከአንድ ደረጃ ወደሌላ በመሸጋገር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከልና የማምረት ኃይሉን በማሳደግና በጥራት በማምረት ገበያውን ወደ መቆጣጠር ያመራል። በዚህ መልክ በተለያየ መስክ የተሰማሩ ካፒታሊስቶች በውድድር ዓለም ውስጥ በመክነፍ ሳያውቁት ሰፋ ላለ ገበያ መዋቀር ውስጠ-ኃይል ይሰጡታል። ከተለያዩ ተጨባጭ ምርትን ከማያመርቱ፣ እንደ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ከተለያየ የንግድ መስክ ጋር በመቆላለፍ ካፒታሊዝም ሁለንታዊና ህብረተሰቡን እንዲቆጣጠር ያደርጉታል። ካፒታሊዝም ከዚህም በማለፍ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ ገበያንና የጥሬ-ሀብትን ወደ መቆጣጠር ያመራል። በራሳቸው ኃይል ሊቆሙ የማይችሉ ህብረተሰቦችን በመቆጣጠር የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት አምራቾችና አቀባዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በዚያውም ቀጭጨው እንዲቀሩ በማድረግ አረማመዳቸውን ይወስናል። የካፒታሊዝምን ሁለንታዊነትና እንቅስቃሴ  ለመረዳት ከታቻ የሰፈረውን ግራፊክ መመልከቱ ተቀራራቢ ስዕል ይሰጠናል።

 

 

ከ1950ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ የተሳሳተ ፖሊሲ መከተል የጀመሩት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች እዚያው በዚያው በድህነት ህዝባቸውን የሚያሰቃዩት ይህንን የአውሮፓውን የዕድገት ፈለግና የካፒታሊዝምን ምንነት ባለመረዳት ነው። ከምትክ የኢንዱስትሪ ተከላ ጀምሮ፣ እስከ ቤዚክ ኒድስና፣ የመዋቅር መስተካከያ ፕሮግራም(Structural Adjustment Program(SAP)) ድረስ በአፍሪካ ምድር ውስጥ ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ሀብትን የሚፈጥሩና ዕድገትን የሚያመጡ ሳይሆኑ፣ ድህነትን የሚፈለፍሉ ናቸው። በአገራችን ምድርም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆን ድህነት በታሪካችን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲመረት ሊደረግ በቃ። በደሀና በሀብታም መሀከል ከፍተኛ ልዩነት እንዲፈጠር በማድረግ ሰፊው ህዝብ እየተገፋና እየተሰቃየ እንዲኖር ተደረገ።

በአገራችን ምድር ዛሬ የሰፈነው እጅግ የሚያሳዝንና የሚዘገንን ድህነት፣ የህዝባችን አስከፊ ኑሮ ከግሎባል ካፒታሊዝም ደካማ አገሮችን አቆርቁዞና አደህይቶ ከማኖር ስትራቴጂ ተነጥሎ ሊታይ በፍጹም አይችልም። ይህ ያልገባው፣ ወይም ገብቶት ለውይይትና ለክርክር፣ እንዲሁም ህዝብን ለማስተማር ዝግጁ ያልሆነ ሰው እንዲያው በደፈናው አገሬ አገሬ፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ቢጮህ ዋጋ የለውም። ዝም ብሎ የሰውን ጆር ከማደንቆር በስተቀር የሚፈጥረው ነገር የለም። ይህ ግንዛቤ ውስጥ ከገባ በመሰረታዊ ነገሮች ላይ መነጋገር እንችላለን። በዚህ ላይ መግባባት ከሌለ በተለያየ ቋንቋ ስለምንነጋገር ፊናችንን እየለየን መታገል ይኖርብናል ማለት ነው።

ከዚህ በመነሳት ኢኮኖሚስቶች ነን እያሉ እዚህና እዚያ እየተሯሯጡ በተወሳሰበ ሞዴል ራሳቸው ግራ ተጋብተው ሌላውን ግራ የሚያጋቡ፣ የሰው ልጅ ሰለገበያና ስለግብይይት ከማውራቱ በፊት ራሱን ስለመመገብ መጨነቅ እንዳለበት አያሰተምሩም። እንዴት ብዩ ነው ሆዴን ሞልቼ የማድረው? ብሎ ራሱን መጠየቅ እንዳለበት አይነግሩንም። እንደሚታወቀው መኪና ካላቤንዚን ወይም ካለኃይል ለመንቀሳቀስ የማይቸልውን ያህል የሰው ልጅም ለመንቀሳቀስና ለመስራት የግዴታ ምግብ ያስፈልገዋል። ምግብ ለሰው ልጅ ኃይል ሰጭ ነው። በምግብና በውሃ አማካይነት ብቻ ነው ህዋሶቹ ሊዳብሩና ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት። ስለዚህም ለአንድ አገርና ህዝብ ራስን በምግብ መቻል መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ይህ ከፍተኛ ግንዛቤ ውስጥ መግባት መቻል አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ስለገበያ ኢኮኖሚና አወቃቀር መወያየት ይቻላል። የዛሬውም ጥያቄ የገበያን ኢኮኖሚ የመቃወምና ለሱ ጠበቃ ሆኖ መታገል ሳይሆን፣ ይህ ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት የተለወጠውን የገበያ ኢኮኖሚ በማጋለጥ አንዴት ጥበባዊ የሆነ ኢኮኖሚ መግንባት ይቻላል በሚለው ላይ ነው መከራከር ያለብን።

ስለ ማክሮና ሚክሮ ኢኮኖሚክስ የተማረ በደንብ ተገንዝቦት ከሆነ በማንኛውም መጽሀፍ ውስጥ ስለ አገርና ህበረተስብን ስለመገንባት ጉዳይ በፍጹም አይወራም። በማክሮና በሚክሮ ኢኮኖሚክስ እመለካከት አገርና ህብረተሰብ በፍጹም አይታወቁም። ሁሉም ነገር ወደ ገበያነት ስለሚለወጥ ሁሉም ሰው ህልሙንና ምኞቱን በገበያ አማካይነት ብቻ ነው ተግባራዊ የሚያደርገው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሚክሮና ማክሮ ኢኮኖሚክስ ስለፍጆታ አጠቃቀም፣ ስለሞኔተሪና ስለፊስካል ፖሊሲ ነው እንጂ የሚያወሩት ስለምርት ማምረት፣ ስለ ሳይንስና ስለ ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት አንዳችም ቦታ አይነግሩንም። የሚክሮና የማክሮ ኢኮኖሚክስ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ የንግድ ልውውጥ ነው። ራሱ የኢኮኖሚክስ ፍልስፍና አባት በመባል የሚታወቀው አዳም ስሚዝ የሚያነሳቸው መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች አሉ። ይኸውም የስራ-ክፍፍልና የማሺነሪን አስፈላጊነት ነው። ቻርለስ ባቤጅ የሚባለው የ18ኛው ክፍለ-ዘመን ታላቅ ኢንጂነር ስለ ኢኮኖሚክስ ኦፍ ማሺነሪ በሚለው መጽሀፉ ውስጥ አጥብቆ የሚያነሳው ካለማሺን አጠቃላይና ሁለ-ገብ የሆነ የምርት እንቅስቃሴን ማካሄድ እንደማይቻል ነው። ማርክስና ሹምፔተርም ይህንን አስተሳሰብ ያሰምሩበታል። ካለቴክኖሎጂ ምጥቀት ሰለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለሀብት ፈጠራ ማውራት አይቻልም። ስለዚህም ይላል ሹምፔተር፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደክንዋኔ መታየት ያለበትና ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለውና ሁሉንም የሚያዳርሰው። ለዚህም ደግሞ የኢኮኖሚን ውስጣዊ ህግ ማውቅ ያስፈልጋል። ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔና ዕድገት ፊዚካላዊ፣ ኬሚካላዊና ባዮሎጂካል ክንዋኔ የሚያጠቃልል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህም ማለት አንድ ነገር በሀይል አማካይነት ብቻ ነው ከአንድ ጥሬ ሁኔታ ወደ ፍጆታ ወይም ጠቀሜታነት ሊለወጥ የሚችለው። በምርት ክንውን ውስጥ ፊዚካላዊና ኬሚካላዊ ለውጦጭ ይካሄዳሉ። ማንኛውም ነገር በምርት ክንውን ውስጥ የመጀመሪያውን ወይም ጥንታዊ ቅርጹን በማጣት ወደ ፍጆታነት በመለወጥ የሰውን ልጅ ፍላጎት ያሟላል ማለት ነው። ምርት በየጊዜው በከፍተኛ ደረጃ ይመረት ዘንድ የኃይል ማመንጨት ሁኔታና ዐይነት አየተሻሻለና ብቃትን እያገኘ መምጣት ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው። በሌላ አነጋገር በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪና በባዮሎጂ ላይ ርብርቦሽ ከሌለ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትና ክንዋኔ ማውራት አይቻልም። ሁሉም ነገር በፊዚክስ አማካይነት ብቻ ነው መዳበር የሚቻለው። መካኒካል እነርጂ፣ የሙቀትና የኤሌክትሪካል ኢነርጂ፣ መካኒክስ፣ ኦፕቲክና ፋይን መካኒክስ፣ እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስ የፊዚክስ መሰረተ-ሃሳቦችና የኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ነገሮች ናቸው። ስለዚህም ካለተፈጥሮ ሳይንስ ስለኢኮኖሚና ስለ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። በተለይም በፊዚክስ አማካይነት ነው በአንድ አገር ውስጥ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትን ማዳበር የሚቻለው።

ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት መሰረተ-ሃስባች በመነሳት እንዴት አድርገን የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር መፍታት ይቻላል? ብለን መወያየት አለብን። በመጀመሪያ ግን የኢትዮጵያን ህዝብ በሚያንገበግበው  መሰረታዊ፣ በተለይም በምግብ ላይ አትኩሮ መስጠት ያስፈልጋል። ዛሬ ህዝቡን አላላውስም ብሎ አንቆ የያዘውን የኑሮ ውድነት ላይ በሚገባ መወያየት አለብን። የችግሩን ዋና ምክንያት ማወቅ አለብን።  የምግብ መሰረታዊ ጥያቄ ሲፈታለት ብቻ ነው ህዝባችን አገሩን አገሬ ብሎ ሊጠራ የሚችለው። በጋራም እጅ ለእጅ ተያይዞ አገሩን መገንባት የሚችለው።

አሁንም ከታሪክ በመነሳት የአውሮፓውን የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ስንመለከት በየወቅቱ የነበሩት አገዛዞች ቅድሚያ ይሰጡ የነበረው የምግብን ጥያቄ ለመፍታት ነበር የሚሯሯጡት። ከዚያ በመነሳት ነው ቀስ በቀስ ወደሚቀጥለው ደረጃ መተላለፍ የቻሉት። ይሁንና ግን ሌሎች ነገሮችም እዚያው በዚያው ጎን ለጎን ይካሄዱ እንደነበር ግልጽ ነው። የነሱን የዕድገት ስትራቴጂ ስንመለከት አካሄዳቸው ሁለ-ገብ(Holistic)ነበር። የገበያ ኢኮኖሚ እያሉ የተሯሯጡብት ወቅት አልነበረም። በሌላ ወገን ግን የገበያን ኢኮኖሚ ክንዋኔ ከውስጡ አጠቃላይ ዕድገት ነጥለው ያዩበት ጊዜ አልነበረም። በጊዜው በምሁራን ዘንድ ይታወቅ የነበረው የውስጥ ገበያ(Home Market) የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ ነበር። ይህም  ደግሞ ከአጠቃላዩ ህብረተሰብአዊ ክንዋኔና ዕድገት ተነጥሎ የሚታይ አልነበረም።

ያም ሆነ ይህ በአገራችን ውስጥ የምግብን ችግር እንዴት መፍታት እንችላለን? በሚለው ላይ ውይይት ማካሄድ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የየካቲቱ አብዮት ይዞ ከተነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የመሬት ለአራሹን ጥያቆና ሪሶርስን የመቆጣጠር ጉዳይ እንደመነሻ መውሰድ አንችላለን። በመስረቱ የዚያን ጊዜው ጥያቄ ትክክልል የሆነውን ያህል በነበረው የፖለቲካ ትርምስ ምክንያት የተነሳ በትክክል የተመለሰ አይደለም። ይህም ማለት ገበሬው በቂ መሬት ማግኘት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በተለያየ መንገድ የራሱን ምርት ተቆጣጣሪ መሆን አልቻለም። በተጨማሪም የመሬት ለአራሹን ጥያቄ በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉት የኢንስቲቱሽን፣ የማቴሪያልና የገንዘብ ድጋፍ በሚገባ አልተዘጋጀም ነበር፤ ወይም ደግሞ በጊዜው የፖለቲካ ትርምስና ግብግብ የተነሳ እነዚህ ነገሮች ደረጃ በደረጃ እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ለማጤን ጊዜ አልተገኘም ነበር ማለት ይቻላል።  ወያኔ/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋለ ይህንን ችግር ለመፍታት የወሰደው እርምጃ የገበሬውን የማምረት ኃይል የሚያዳክም ነበር። በመጀመሪያው ወቅት ገበሬው በበቂው እያመረተ ገበያ ላይ አምጥቶ ሊሸጥ ሲል ከውጭ በመጣና በርካሽ በሚሸጥ ስንዴና በቆሎ ጋር ይጋፈጥ ስለነበር ምርቱን ማፍሰስ ብቻ ሳይሆን፣ የምርቱንም ሂደት ወደማቀዝቀዝ ተገፋ። ከዚህ በላይ ደግሞ ቡናና ጨአት ነው የሚያዋጣው እየተባለ መወራት ስለተጀመረ፣ አንዳንዱ ወደ ጨአት ተከላ ላይ ተሰማራ። የተቀረው ደግሞ ወደ አበባ ተከላ አመራ። ድሮ ስንዴና ጤፍ የሚመረትባቸው መሬቶች ለውጭ ገበያ ምንዛሪ በማለት ወደ አበባ ተከላነት ተቀየሩ። ይህ በእንደዚህ አንዳለ ገበሬውን በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ ስትራቴጂ የቀየሰው የወያኔ አገዛዝ በእርሻ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ተከላ በሚለው አጉል ፈሊጥ ገበሬውን በዕዳና በደንብ ባልተጠና ዘርና ማደባሪያ እንዲሁም የተባይ ማጥፊያ በመተብተብ ምርት በጥራትም ሆነ በብዛት እንዳይመረት አደረገ። ከዚህ ባሻገር ተግባራዊ ባደረገው የክልል ፖሊሲ የተነሳ በመጀመሪያው ወቅት በኦሮሞ የነፃ አውጭ ግንባርና (OLF) በራሱ በወያኔ ብዙ ገበሬዎች ያለሙትን መሬት ለቀው እንዲሸሹ ተገደዱ። የተቀሩት በግፍ ተገደሉ። ይህ ዐይነቱ ጭፍን አካሄድ በከተማዎች የህዝብ ቁጥርና አዳዲስ የአገልግሎት መስክ እንዲስፋፋ ሲያደርግና ሆቴል ቤቶች በብዛት ሲሰሩ በገጠሩና በከተማ፣ በተለይም በአዲስ አበባ መሀከል ያለው የዕድገት ሁኔታ መዛባትን ፈጠረ። የአዲስ አበባ ከተማ የገጠሬውን የአራሽ ኃይል ሟጣጭ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀብቶችን፣ እንደ እርሻ ውጤት የመሳሰሉትን የሚጋራ ሆነ። በሌላ አነጋገር በተለይም በገጠሩ ህዝብ ላይ የሚመካው አዲሱ መጤ ሀብታም ከገበሬው ሀብት በተለያየ መልክ የሚጋራውን ያህል፣ ለሱ መልሶ በዕውቀት የሚክስበት ዘዴና ፍላጎት አልነበረውም፤ የለውምም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰፊው ገበሬ አሁንም እንደወትሮው በኢንስቲቱሽን የተደገፈ ጥናት፣ የማቴሪያልና የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት አልቻለም። ለገበሬው እርሻ መዳከም ሌላው ምክንያት ገበሬው ለዘሩ በውጭ አቅራቢዎች ጥገኛ እየሆነ በመምጣትና ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የዘር ዐይነት እንዲያጣ መደረጉም ጭምር ነው። የአሜሪካን አገዛዝ የሶስተኛውን ዓለም ህዝቦች በተለይም አፍሪካን ለመቆጣጠር ሲል በሞንሳቶ አማካይነት የዘር ዐይነቶች ስታንደርዳይድ መሆን አለባቸው በማለት የእርሻ ሚንስትሩ ላይ ጫና በማድረግ ብሄራዊ ነፃነታችንን ሙሉ በሙሉ ወደ መግፈፍ በማምራት ላይ ነው። በጊዜው ከወያኔ ጋር የተቆላለፉ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ከውጭ ዘር እያስመጡ ለገበሬው በመሸጥና ገበሬውን ሙሉ በሙሉ ጥገኛ በማድረግ ላይ ነበሩ። ይህ ዐይነቱ የአትራፊነት ስልት በጠቅላላው የእርሻ ባህልና ወደፊት በምንገነባው ህብረተሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር በቅቷል።

በመሰረቱ የኢትዮጵያ ህዝብ መራብና መለመን አልነበረበትም። እንደ ኢትዮጵያም ለእርሻ የሚስማማና የአስር ሺህ ዐመት ዕድሜ የሰብል ተከላ ታሪክ ያለው አገር የለም። በአገራችን ምድር የተለያዩ የስንዴና የጤፍ ዘሮች፣ ገብስ፣ አጃ፣ ማሽላና ዘንጋዳ፣ በቆሎ፣ አተርና ሽምቡራ፣ ባቄላና ቦለቄ፣ ቆጮና ድንች፣ ጎደሬና ወጭኖ እንዲሁም ልዩ ልዩ የስብል ዐይነቶችና ፍራፍሬዎች ይበቅላሉ። በደንብ ከታሰበበትና በሳይንስ ከተጠና ተጨማሪ የሰብል ዐይነቶችንም ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን በብዛት ማምራት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የተለያየ የሰብል ዐይነቶች በሚገኝበት አገርና፣ መሬቱ ለእርሻ በሚያመችበትና ውሃ እንደልብ በሚገኝበት አገር ነው ህዝባችን ከሃምሳ ዐመት በላይ በየአምስት ዐመቱ የሚለምነውና የሚራበው። ይህ ሁኔታ የግዴታ መለወጥ አለበት። ይህንን ለመለወጥ፣ ህዝብቻንን ለመመገብና፣ የተረፈውንም ወደ ውጭ ለመላክና ምንዛሪ ለማግኘት፣ እንደገና መልሶ ለልማት ለማዋል የግዴታ የፖለቲካው ሁኔታ መለወጥ አለበት። የዛሬው የፖለቲካ አወቃቀር እስካልተቀየረ ድረስ ወደ ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች መሸጋገር አንችልም።

የዛሬው የፖለቲካ አወቃቀር ከተለወጠና ሌላ ኃይል ስልጣን ቢይዝ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት በሞኖፖሊ የተያዙ የእህል እንቅስቃሴዎችንና ንግዶችን በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በእርሻ ተግባር ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎችን ማባረርና መሬቱን ለኗሪው ህዝብ መልሶ መስጠት ግዴታ ነው። የእርሻ ተግባርን ማካሄድና መሬትን መንከባከብ ባህላዊ ስለሆነ ከውጭ የመጡ ኢንቬስተር ነን የሚሉ ይህንን ጉዳይ ሊያሟሉ በፍጹም አይችሉም። ከዚህም ባሻገር የውጭ ኢንቬስተሮች ትርፋማ ናቸው በሚላቸው ሰብሎች ላይ ስለሚሰማሩ ለአገር ግንባታ ምንም አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ አይችሉም። ለኩሙኒቲ ዕድገትና ለህብረተሰብአዊ መተሳሰር እንቅፋት ብቻ ሳይሆኑ፣ በገጠር ውስጥ ከእርሻ ጋር የተያያዘ የጎጆ ኢንዱስትሪ እንዳይቋቋምና እንዳይስፋፋ ያግዳሉ። ባጭሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደህዝብና እንደ ህብረተሰብ እንዳይተሳሰርና ጠንካራ አገር እንዳይገነባ ከፍተኛ እንቅፋት ይሆናሉ። በሶስተኛ ደረጃ፣ ማንኛውንም ለህብረተሰቡ የሚያስፈልጉ ምግብና ምግብ ነክ ነገሮች ወደ ውጭ እንዳይላኩ ማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ ደረጃ በደረጃ የገበያ ግልጽነት እንዲኖር አስፈላጊውን የመቆጣጠሪያ መሳሪያና ህግ ማውጣት ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ከአገሪቱ ምርት ጋር የሚወዳደሩ ምግብና ምግብ ነክ ነገሮችን ማገድ፣ በከፍተኛ ደረጃ መቅረጥ፣ ወይም ደግሞ መገደብ እጅግ አስፈላጊ ነው። አንድ አገር የራሷ በቂ ምርት እስካላት ድረስ የግዴታ መግዛት አለብሽ የሚል የተፈጥሮ ህግ የለም። ከዚህ ሌላ ከውጭ የሚመጡ ምግቦች በሙሉ ከኬሚካል ነፃ መሆናቸውን መቆጣጠርና፣ ለዚህ በእርሻ ሚንስተር ስር የሚተዳደር ላቦራቶሪ ማቋቋም ያስፈልጋል። በግል መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ካሉም እነሱን በክሬድትና በምክር መደገፍ።

የእርሻውን መስክ ምርታማና የተለያዩ ስብሎችን ለማምረትና፣ የእርሻ ሰብሉም ለኢንዱስትሪው መስክ የጥሬ-ሀብት አቅራቢ እንዲሆን የግዴታ የእርሻ ሚንስትሩን በአዲስ መልክ ማዋቀርና፣ በየክፍላተ-ሀገራቱም ተመሳሳይ ሚንስትሪዎች እንዲቋቋሙ ማድረግ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የእርሻ መስኩን ምርታማ ለማድረግ የግዴታ ለገበሬውና ለመሬቱ የሚስማማ የማረሻና የእህል መሰብሰብያ ማሽኖችንና መሳሪያዎችን ማመረቻ ፋብሪካ ማቋቋም እጅግ አስፈላጊ ነው። የገበሬውን ምርታማነት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የገበሬውን ድካም ማቃለል የሚቻለው በየጊዜው የተሻሻሉ የማምረቻ መሳሪያዎች ሲቀርቡለት ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር የእርሻው መስክ የግዴታ በአግሮ ኢንዱስትሪ አማካይነት መካሄድ የለበትም። ይህ ዐይነቱ የአመራረት ዘዴ ለእርሻ ባህል ፀር የሆነና፣ ከንፁህ ትርፍ አንፃር የሚካሄድ በመሆኑ በጠቅላላው በመሬቱና በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

ከዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ስንነሳ፣ የሚቀጥሉት የኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎች፣ ንጹህ ውሃ ማግኝት፣ ከጎጆ ቤት መላቀቅ፣ ኃይል ማግኘትና በገጠር ውስጥ አነስተኛና ማዕከለኛ የህክምና ዘዴዎችን ማስፋፋት ናቸው። አብዛኛዎቹ የማዕከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅዶች ሲሆኑ፣ ደረጃ በደረጃ ሊመለሱ የሚችሉና መመለስም ያለባቸው ናቸው። መመለስም ይችላሉ። እነዚህ ጥያዎች ካልተመለሱ ደግሞ ስለአገር ማውራት በፍጹም አይቻልም። በአገራችን ምድር የሚገኙት የጥሬ-ሀብቶችና የሰው ጉልበት ተጨምሮበት ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች መመለስና መልክ ማሲያዝ ያስፈልጋል።  ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሶሻል ፖለቲካ ግንዛቤ ያስፈልጋል። አንድ ህብረተሰብ እንደሰውነታችን በሚሊያርድ በሚቆጠሩ የነርብ ሲስተሞች መያያዝ እንዳለበት ሁሉ አንድም ህዝብ እንደማህበረሰብና እንደህብረተሰብ እንዲደራጅ ከተፈለገ በቀጥታ በግልጽ መወሰድ ያለባቸው ነገሮች አሉ። አንድ አገር በማንኛውም የውጭ ኃይል ሊፈራና ሊከበር የሚቸለው በውስጥ ባለው ዕድገትና መተሳሰር፣ ውብ በሆኑ ከተማዎችና መመላለሻዎች ሲተሳሰር ብቻ ነው። ይህንን መረዳት ካልተቻለ ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን ማለት ነው። ዛሬ መስመር ካልያዘ የዛሬ ሁለት መቶ ዐመትም ሊመለስ አይችልም ማለት ነው።

ከዚህ ተነስተን ወደ ሀብት ማዳበሪያ ወይም ማበልጸጊያ ዘዴዎች ስንመጣ ከአውሮፓ ፈላስፋዎችና የህብረተሰብ ታሪክ የምንማረው ቁም ነገር አለ። በመጀመሪያ ለአንድ አገር ዕድገት ጭንቅላትና የጭንቅላት መዳበር የሚይዙትን ከፍተኛ ቦታ መገንዘብ ያስፈልጋል። የግሪክም ሆነ የአውሮፓ ፈልሳፋዎች የዕውቀትና የፈጠራ፣ እንዲሁም የሀብት ምንጭ ዋናው ነገር የሰው ልጅ ጭንቅላት ወይም ማይንድ የሚሉት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ፍላጎት ወም ዊል(Will) የሚሉት ነገር አለ። እነዚህ ሁለት ነገሮች ሲጣመሩ ተራራንም መግፋት ይቻላል ይባላል።

ከዚህ በተረፈ በኢኮኖሚስቶች ዘንድ የሀብት ምንጭን በሚመለከት ክርክር ተካሂዷል። የመጀመሪያዎቹ ኢኮኖሚስቶች፣ ፊዚዮክራትስ ተብለው የሚጠሩ እርሻንና ገበሬውን ዋናው የሀብት ምንጭ አድርገው ይወስዱ ነበር። በጊዜው የነበሩበት ሁኔታ ከዚህ ርቀው እንዲያስቡና እንዲሄዱ ሊያደርጋቸው አልቻለም። ምክንያቱም በፊዚዮክራቶች ዘመን አብዛኛው የአውሮፓ ህዝብ በግብርና የሚተዳደርና በእርሻ ምርት ላይ ጥገኛ የሆነ ነበር።  በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት መርካንትሊስቶች የሚባሉት ኢኮኖሚስቶች ደግሞ ለአንድ አገር ዋናው የሀብት ምንጭ በውጭ ንግድ አማካይነት የሚገኝ የወርቅና የብር ክምችት ነው ብለው ያምኑ ስለነበር፣ ብዙ ወርቅና ብር ለማግኘት የነቃ የውጭ ንግድ ፖሊሲ መካሄድ እንዳለበት ነገስታቱን ያማክሩ ነበር። በዚህ መሰረት አንድ አገር ከውስጥ ገበያዋን ስትከላከል ወደ ውጭ ደግሞ በብዛት መሸጥ አለባት። ይሁንና ግን መርካንትሊስቶች በዚህ ሳይወሰኑ የውስጥ ገበያን ለማስፋፋት መንግስታት ንቁ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል እንዳለባቸው ያስተምሩ ነበር። አነ አዳም ስሚዝ ብቅ ሲሉ፣ ዋናው የሀብት ምንጭ ስራ መሆኑ ተደረሰበት። ማርክስ ይህንን በማስተካከል፣ ስራ የዋጋ ምንጭ ሲሆን፣ ስራና ተፈጥሮ ወይም በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኝ ነገሮች ተደምረው ህብረተሰብአዊ ሀብት መፍጠር ይችላሉ ይለናል። ከዚህ ወጣ ስንል ሳይንስ እየዳበረ ሲመጣ፣ የሰው ልጅ ጥረት፣ ኃይልና ቴክኖሎጂ ዋናው የሀብት ማመንጫ ዘዴዎች ናቸው ወደሚለው ድምዳሜ ውስጥ ተደረሰ። እነዚህ ሁሉ በየጊዜው ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የዳበሩ አስተሳሰቦችና የሚደጋገፉ ናቸው። አንደኛው ትክክል ነው፣ ሌላው ስህተት ነው ብለን መከራከር አንችልም። ይሁንና ግን ሁሉም ቢሆን ለኢኮኖሚና ለህብረተሰብአዊ ዕድገት የጭንቅላት ሚና ከፍተኛ ቦታ ይሰጡታል። ገንዘብና የጥሬ ሀብት ተትረፍርፎ ቢገኝም ካልታወቀበት እንደናይጄሪያና አንጎላ ድህነት መፈልፈል ይቻላል። ስለዚህም ትክክለኛ ዕውቀትና ፍላጎት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ ማለት ነው። ይህንን የሀብት አፈጣጠር ዘዴ በሚቀጥሉት ዲያግራሞች እንመልከት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ከዚህ ስንነሳ ማኑፋክቱር በአንድ አገር ዕድገት ውስጥ ያለውን ቦታ ማስመር ያስፈልጋል። የማኑፋክቱር እንቅስቃሴና ዕድገት ከእርሻ ጋር ሲወዳደር በጣም ከፍ ያለ ብቻ ሳይሆን የማባዛት ኃይሉም ከፍተኛ ነው። ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት እርሻ በማደባሪያና በማሽን ተደግፎ ስለሚሰራና፣ አንድ መሬትም በተደጋጋሚ የሚታረስ ከሆነ ውጤቱ እያደገ ሳይሆን እየቀነስ(Deacreasing returns) የሚሄድ ነው። የማኑፋክተርን ትርጉም፣ የማደግና እንዲሁም የመስፋፋት ኃይል የተገነዘቡት የአውሮፓ መንግስታት ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ከፍተኛ ርብርቦሽ ያደረጉት በእርሻ መስክ ላይ ሳይሆን በማኑፋክቱር መስክ ላይ ነው። ይህንን አትኮሮና ትክክለኛ ፖሊሲ ፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርት፣ ሀብታም አገሮች ለምን ሀብታም ሆኑ፣ ደሃ አገሮች ለምን ደሃ ሆነው እዚያው ቀሩ በሚለው መጽሀፋቸው ውስጥ እንደዚህ በማለት ያሰቀምጣሉ።“European observed early on that generalized wealth was found only in areas where agriculture was absent or only played a marginal role, and came to be seen as unintended by-product when many diverse branches of manufacturing were brought together in large cities. Once these mechanisms were understood, wise economic policy could spread wealth outside these few `naturally wealthy `areas.  Policies of emulation could, indeed, also spread wealth to formerly poor and feudal agricultural areas, but they involved massive market interventions. For laggard nations market interventions and wise economic policies could substitute the first wealthy states. We can further imagine that export taxes on raw materials and import taxes on finished products were originally means for increasing revenues in poor nations, but that a by-product of these measures was to increase wealth through the growth of domestic manufacturing capacity.This blend of purposes was already clear in England under Eduard III (1312-77)”   Prof. Erik S. Reinert, How Rich Countries Got Rich … and Why Poor Countries Stay Poor, London, 2007 P. 17)

ስለሆነም አንድ አገር እንድታድግ ከተፈለገ የግዴታ የማኑፋክቱር አብዮት ማካሄድ አለባት። ይህንን ለማድረግ የግዴታ ከመጀመሪያውኑ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ መረባረብ የለባትም። እንደዚህ ዐይነቱንም አካሄድ ልንቆጣጠረው ወደማንችለው ቦታ ይወስደናል። በመጀመሪያ ደረጃ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ መረባረብ ያለብን። እነዚህ የግዴታ በብረታብረትና በማሽን ፋብሪካ፣ ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎችን ዲዛይን በሚያደርጉ ኢንስቲቱሽኖች ወይም ኢንዱስትሪዎች መደገፍ አለባቸው። በመሰረቱ በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ(Knowledge based) መሆን ሲገባቸው፣ በአገር ውስጥ የጥሬና የሰው ኃይል(Resource based) የሚንቀሳቀሱ መሆን አለባቸው። ከዚህ ጋር በማያያዝ ያሉትን ኮሌጆች ወደ ቮኬሽናል ትምህርት ቤቶች በመቀየር፣ ማንኛውም ተማሪ ከ12ኛ ክፍል በኋላ በተከታታይ በማንኛውም ቴክኖሎጂ ነክ ነገሮችና የሳይንስ ስልጠናዎች አምስት ዐመት ሙሉ በተከታታይ እንዲሰለጥን ማድረግ። ከዚህ በኋላ የፈለገው በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲት ይገባል፣ ሌላው ደግሞ ወደ ስራ መስክ ላይ ይሰማራል። በአጭሩ ትምህርቱ ተግባራዊና ፈጣሪ የሚያደርግ መሆን አለበት። ከተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር መያያዝ አለበት። በየኮሌጆችና በየቮኬሽናል ትምህርት ቤቶች በቂ መለማመጃዎችና ላቦራቶሪዎች መቋቋም አለባቸው። በቂ መጻህፍት ቤቶች፣ በተለይም በአማርኛ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መጻህፍት እየተተረጎሙ መቅረብ አለባቸው። ለዚህ የሚሆን ሰፋና ትልቅ የምርምርና የመተርጎሚያ ላይብረሪ ለብቻው መቋቋም አለበት። አስፈላጊው መጽሀፎች ከውጭ እየመጡ መተርጎም አለባቸው። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ዕወነተኛ ዕድገትን ማምጣት የምንችለው፤ ረሀብንና ድህነትንም ማጥፋት የሚቻለው።

ይህ መሰረተ ጉዳይ ሲሆን፣ አሁን ያለውን ስራ-አጥ ህዝብና ወጣት በስራ ለማሰማራት ዘዴዎች መፍጠር ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ያሉት ኢንዱስትሪዎች ለዚህ ሁሉ ስራ ፈላጊ የስራ መስክ ሊፈጥሩ አይችሉም። ያለው አማራጭ በኢንስቲቱሽን የሚደገፍ ከስልጠና ጋር የሚያያዝ የስራ መስክ መክፈት ይቻላል።  ሰራተኛውን ወጣቱ በተለያዩ ሙያዎች በሳምንት ሁለት ቀን ኮርስ ይሰጣቸዋል። በተቀረው ሶስት ቀን ፕራክቲካል ስራዎችን በማዘጋጃቤትና በተቀሩት ኢንስቲቱሽኖች በሚዘጋጁት፣ እንደግንብ ስራ፣ እንደ መንገድ ስራ፣ እንድ ጋርደንና የዛፍ ተከላዎች በመሰማራት ጊዜያቸውን ሊጠቀሙበትና ለህብረተሰቡም ሀብት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይህ ዐይነቱ ፕሮግራም በምግብ ለስራ በሚባል(Food for Work) ፈንድ ሲደገፍ፣ በዐይነትና በምግብ እንዲሁም በዘይትና በአንዳንድ የፍጆታ መልክ ይከፈላል። በዚህ መልክ ከ18 ዐመት ዕድሜ በላይ አንስቶ እስከ 60 ዐመት ዕድሜ ድረስ ያለውን የሰው ኃይል ማንቀሳቀስ ይቻላል። በእኔ ዕምነት ይህ መንገድ ብቻ ነው ያለንን ችግር እንድንቀርፍ የሚረዳን። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች ሰማንያ በመቶ ያህሉን የፈራረሰውን ህንፃዎቻቸውንና ኢኮኖሚያቸውን በ15 ዐመት ውስጥ መልሰው መገንባት የቻሉት ህዝቡን ለስራ በማንቀሳቀስ እንጂ በተራ የገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት አይደለም።

ይህንን ከተመለክትን በኋላ የገበያ ኢኮኖሚ እያሉ ለሚጮሁት ግራ እንዳይጋቡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሶስት መልከ ማዋቀር ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የመንግስት ሚና ግልጽ ሆኖ መቀመጥ አለበት። ግለሰቦች ሊሳተፉባቸው በማይችሉባቸው መስኮች ሁሉ የመንግስት ሚና ግልጽ ይሆናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ በጋርዮሽ ወይም በአክሲዮን መልክ ወይም በሌላ መልክ ሊቋቋሙና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የአደረጃጀትና አመራረት ስልትን ማጥናት ይቻላል። በሶስተኛ ደረጃ ግለሰብ ከበርቴዎች ወይም ኢንቬስተሮች የሚሳተፉበት ሁኔታ መዘጋጀት አለበት። ለዚህ ደግሞ ትናንሽና ማዕከለኛ ባለሀብታሞችን በየትና በምን መስክ ላይ መሰማራት እንደሚችሉ ምክር የሚስጥ ኢንስቲቱሽን መቋቋም አለበት። እዚህ ላይ መንግስት አጋዥ እንጂ የሚቀናቀናቸው መሆን የለበትም። በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚካሄዱ ኢንዱስትሪዎችም ሆነ ልዩ ልዩ ሀብቶች የህዝብ መሆናቸው በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። መንግስት አገልጋይና ሁኔታዎችን የሚያመቻች መሆን አለበት። ሀብት እየፈጠረም ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ የኃይል ማመንጫ ዘዴዎቻ፣ የውሃ ቧንባዎችን፣ መንገዶችንና መመላለሻዎች እንዲስፋፉና እንዲዳብሩ ድጋፍ መስጠት አለበት።

ይህንን ከተመለከትን በኋላ ይህንን ሁሉ እንዴት ፋይናንስ እናደርገዋለን የሚለው ጥያቄ ይነሳል። እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በአገራችንም የገንዘብንና የፋይናንስን ጉዳይ በሚመለከት ትልቅ መወናበድ ይታያል። ይህም የሆነበትም ምክንያት ስለገንዘብ ሎጂካዊ ዕድገት ያለን አስተሳሰብ የተዛባ በመሆኑ ነው። ስለሆነም የአንድን አገር ዕድገት ከዶላር ወይም ዛሬ ደግሞ ከኦይሮ ጋር በማያያዝ ብቻ ነው ዕድገት ሊመጣ ይችላል የሚችል የተሳሳተ አባባል በመስፋፋቱ ብዙውን አሳስቷል። ባለፉት ስላሳና አርባ ዐመታት የውጭ ዕዳን በሚመለከት በብድር አማካይነት ዕድገት እናመጣለን ያሉ አገሮች በመሉ ወደ ድህነትና ኢኮኖሚያቸውን ወደ ማዘበራረቅ ነው ያመሩት። የመጨረሻ መጨረሻም እስከዛሬም ድረስ የወለድ ወለድ ከፋዮች በመሆን ንጹህ ሀብታቸውን ለኢንዱስትሪ አገሮች ያስተላልፋሉ። ለምሳሌ እንደናይጀሪያና አንጎላ የመሳሰሉት በዘይት ሀብት፣ በወርቅና በዲያመንድ የተትረፈረፉ አገሮች ለምን ብድር እንደሚያስፈልጋቸው አይገባኝም። ለምንስ ለዕድገታቸው ከሚያስፈልጋቸው በላይ ዘይት እያመረቱ የአካባቢ ውድመትና መመረዝ እንደሚያስከትሉና ችግር ውስጥ እንደሚገቡ በፍጹም ግልጽ አልሆነልኝም። ማለት የሚቻለው ግን ከሙስና ባሻገር እነዚህ መንግስታት በውጭ የኮንሰልቲንግ ኩባንያዎችና በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖችና ዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው እየተመከሩ አገሮቻቸውን ወደሲኦልነት እየለወጡ ነው።

ያም ሆነ ይህ ልክ እንደማንኛውም ምርት ገንዘብም የሰው ልጅ ጭንቅላትና የስራ ክፍፍል ውጤት ነው። ከስራ-ክፍፍልና ከንግድ በፊት ገንዘብ አልነበረም። የተለያዩ የገንዘብ ዐይነቶችም መፈጠር የቻሉት የስራ-ክፍፍል ውስብስብ እየሆነ ስለመጣ ነው። ይህም ማለት የዛሬው በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአገሮች ውስጥ የሚታተመው፣ ወይም ደግሞ ውጭ እየታተመ የሚገባው የወረቀት ገንዘብ- በቴክኖሎጂ ምክንያት የተነሳ፣ ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ገንዘብ በቀላሉ ፎርጅ እንዳይደረግ የሚያስላቸው የማተሚያ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል የላቸውም-  የታሪክ ውጤትና አስፈላጊነት ነው። ይህም ማለት የዛሬው የወረቀት ገንዘብ በየመንግስታቱ ወይም በማዕከላዊ ባንኮች ካለምንም ድጋፍ በዕምነት ብቻ እየታተመ እንደ አስፈላጊነቱ እንዲሽከረከር የሚደረግ ነው። ስለሆነም የገንዘብ መጠኑ በኢኮኖሚ ውስጥ በሚመረተው ምርት አማካይነት እየተመጠነ ይሽከረከራል። በሌላ ወገን ደግሞ በተለያዩ መሳሪያዎች አማካይነት ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የተሽከረከረው ገንዘብ ወደባንኮች ይመለሳል። በባንክ፣ በተጠቃሚው፣ በነጋዴውና በአማርቹ መሀከል በገንዘብ አማካይነት መተሳሰር ይፈጠራል። እንደ ኢኮኖሚው ዕድገት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ መመረትና አለመመረት፣ እንዲሁም የውስጥ ገበያ መስፋፋትና አለመስፋፋት፣ መዳበርና አለመዳበር የገንዘብም ጥንካሬና አለመጠንከር ይወሰናል። በአንድ አገር ውስጥ የገንዘቡ የመግዛት ኃይል ደካማ ነው ሲባል፣ ኢኮኖሚው በደካማ መሰረት ላይ ሰለተገነባና ለገንዘቡ የጀርባ አጥንት መሆን ስለማይችል እንጂ፣ ገንዘብ በራሱ የመግዛት ድክመት የለውም። የዋጋ ግሽበትም ዋናው ምንጭ የኢኮኖሚ ድክመት፣ የአመራረት ዘዴ፣ በተመጣጠነ ዋጋ አለማምረት (Cost Effectivness) የጥሬ-ሀብቶችና የስራ ዋጋ መወደድና፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ በገበያ ላይ የሚቀርበው ምርት ዕጥረትና ሌሎች በዓለም ገበያ ላይ የሚከሰቱና በእኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ፣ ወዘተ… ለዋጋ ግሽበት ወይም መወደድ ምክንያት ይሆናሉ። በዚህ መልክ ብቻ ስለገንዘብ የመግዛት ኃይል ወይም ድክመት ማውራት ይቻላል። ገንዘብ ታትሞ ኢኮኖሚ ውስጥ ቢበተን ወይም ከላይ ሆኖ በሄሊኮፕተር ቢበተን የግዴታ ይህ ጉዳይ ለግሽበት ምክንያት ሊሆን አይችልም። በሌላ ወገን የተበተነውን ገንዘብ ከፍተኛ ኃይል ባለው ቫኪዩም ክሊነር ከላይ ሆነን የተወሰነውን ገንዘብ ብንመጠውና፣ ከመሬት ላይ ደግሞ ያለውን የምርት መጠን ካልጨመርነውና (Ceteris Paribus) በድሮው መጠን ብቻ የሚቀርብ ከሆነና የሰፊው ህዝብ የመግዛት ኃይል ካልጨመረ ድረስ ወይም በድሮው መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ይህ ማለት የዕህል ዋጋ ይቀንሳል ማለት አይደለም። ለዛሬው በአገራችን ውስጥ የዋጋ ግሽበት ዋናው ተጠያቄ አገዛዙ ከሃያ ሰባት ዐመት ጀምሮ የሚያካሂደው በዘረፋ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በዚህም የተነሳ አጠቀላይ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አለመኖር፣ የአገልግሎቱ መስኩ መስፋፋት፣- የተጨባጭ ኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያንፀባርቅ ወይም የሱ ተቀጥያ አይደለም- የትላልቅ ሆቴል ቤቶች መስፋፋትና እህል፣ ስጋና ቅቤ፣ ውሃና ሃይል እንዲሁም ልዩ ልዩ ለህዝቡ የሚጠቅሙ ነገሮችን በከፍተኛ ደረጃ መጋራት፣ አዲስ መጤና ገንዘብ ያካበተ ኃይል የፍጆታ አጠቃቀም ከአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሳይመጣጠን መጨመር፣ የውጭ ተራድዕ ድርጅቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሰራተኞች ቁጥር መጨመርና ተጠቃሚ ኃይል መሆን፣ እነዚህ ሁሉ ሲደመሩ የዚህ ዐይነቱ የፍጆታ አጠቃቀም በምርት ዕድገት አለመካካስ ወዘተ… ለዋጋ ውድነት ተጠያቂዎች ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

እዚህ ላይ ለማለት የምፈልገው በገንዘብ ላይ ግልጽ አመለካከትና ሎጂካዊ ዕድገቱን ከተረዳን ስለኢኮኖሚ ዕድገትም የሚኖረውን ሚና መገንዘብ ይቻላል ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ ባንኮችን እንዴት ማደራጀት አለብን? እንዴትስ ለኢኮኖሚ ዕድገት ሊያግዙ ይችላሉ? በምንስ መልክ አምራቹም ሆነ ነጋዴው በቂ የብድር ገንዘብ በዝቅተኛ ወለድ በመበደር ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋፅዖ ማድረግ ይችላሉ? የሚለውን በቀላሉ መመለስ ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ማዕከለኛ ባንክ አለ። ይህ ገንዘብ የሚያትምና ለባንኮች በትንሽ ወለድ የሚያከፋፍል ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በግል የሚንቀሳቀሱ የንግድ ባንኮች የሚባሉ አሉ። በሶስተኛ ደረጃ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር፣ በክፍላተ-ሀገራትና በሎካል ደረጃ ለማዕከለኛና ለትናንሽ ኢንዱስትሪዎች ብድር የሚያበድሩ ይኖራሉ። ከማዕከላዊ ባንክ የገንዘብ ክፍፍል ባሻገር እነዚህ ሁለቱም የባንክ ዘርፎች በመያዣ (Bond) መልክ ወለድ በመክፈል ገንዘብ ካለው በመበደር እንደገና ብድር ለሚፈልገው ገንዘብ ያበድራሉ። ከዚህ በተጨማሪ በደሞዝ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ገንዘቡን በባንክ አማካይነት ያገኛል። የተወሰነውን ደግሞ በቁጠባ መልክ ያስቀምጣል። አስቸጋሪው ነገር በአገራችን ውስጥ አብዛኛው ሰራተኛ በባንክ አማካይነት ደሞዙ አይከፈለውም። አብዛኛውም የመቆጠብ ኃይሉም ደካማ ነው። ስለዚህም የማዕከላዊ ባንኩና የተወሰነው ሀብታም የህብረተሰብ ክፍል ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋፅዖ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ማለት ነው። ከዚህ በተረፈ የውጭ ምንዛሪን መቆጣጠርና ለኢኮኖሚው ዕድገት ብቻ እንዲውል ማድረግ። ለማሽንና ለቴክኖሎጂ እንዲሁም ለጥሬ-ሀብት ማስመጫ ካልሆነ በስተቀር ለቅንጦት እየተባለ የውጭ ምንዛሪ እንዳይባክን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ የጥሬ ሀብቶችን በመላክ  የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት የአገር ውስጥ ገንዘብ ነው ውሳኙ። ዶላርና ኦይሮ አይደሉም። ከዚህ በመነሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ዕድገት የሚነፍሰውን የተሳሳተ አባባል በመጠኑም ቢሆን እንመልከት።

 

ምን ዐይነት ዕድገት፣ ዕድገት ለማን!

እስከዛሬ ድረስ በአገራችን ምድር አንዳች ዐይነት ዕድገትን ለማምጣት ተብለው ተግባራዊ የሆኑ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች በሙሉ በውጭ ኃይሎች የታቀዱና የጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ብቻ የሚያንፀባርቁ ናቸው። በተለይም ግሎባል ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ ካለፉት 60 ዓመታት ጀምሮ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተግባራዊ የሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ በአወቅሁኝ ባይነት የተካሄዱና አሉታዊ ባህርይ ያላቸው ናቸው። የየአገሮችን ታሪክ፣ ባህል፣ የዕውቀት ደረጃና የምጣኔ ሀብት ግኝት በማጥናት የተከናወኑ አይደሉም። በመሰረቱ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተዋቀረውን የዓለም ኢኮኖሚ እንዲያግዙ ሆነው የተዘጋጁ ሞዴሎች በመሆናቸው ሀብትን መጣችና አውዳሚ ሊሆኑ በቅተዋል። በዚህም ምክንያት በየአስር ዐመቱ ስማቸውን እየለዋወጡ የሚወጡት ፖሮግራሞች የባሰውን ድህነትን ፈልፋይ በመሆን ለሀብት መባከንና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መሞትና መሰደድ ምክንያት ሆነዋል። የባሰውኑም ጥገኛ በማድረግ ለብሄራዊ ነጻነት መቦርቦርና ለግለሰብአዊ ነጻነት እጦት ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል። ዛሬ በየአገሮች ውስጥ አገራችንም ጨምሮ አምባገነን መንግስታት የሰፈኑትና በአስፈሪ መሳሪያ በመታጠቅና በተወሳሰበ የስለላ ድርጅትና መሳሪያ የሚያሰቃዩት በየአገሮቹ ውስጥ የፈለቁ ሳይሆኑ ከውጭ በመጣ መሳሪያና በውጭ ኃይል በመታገዝ ነው። ይህም ማለት ከውጭ በዕድገት ስም የሚመጣው ፖሊሲ ከኢኮኖሚ አልፎ ብሄራዊ ነፃነትንና የግለሰብ ነፃነትን በመግፈፍ ለዘለዓለማዊ ድህነት የሚዳርግ ነው። በመሆኑም እስከዛሬ ድረስ፣ በተለይም ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመጨቆኛ መሳሪያዎችና ስልቶች ጋር በመጣመርና ሰፊውን ህዝብ፣ በተለይም የከተማውን ህዝብ በነፃ ገበያ ስም በማታላል የጭቆና ኢኮኖሚን ያስፋፋና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት እንዳይኖር እንቅፋት የሆነ ነው።

ከዚህ ቀደም አንዳንድ ቦታ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት አገራችን እስከዛሬ የተከተለችውና ወደፊትም መከተል የሚገባትን የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ፖሊሲ በሚመለከት በምሁሩ ዘንድ ውይይት፣ ጥናትና ክርክር ሲካሄድ በፍጹም አይታይም። አብዛኛው ማለት ይቻላል፣ የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ስታትስቲኮችን ከማገላበጥ አልፎ ለአገሩ ጠበቃ በመሆን በአገር ወዳድነት ስሜት ትንተና ሲሰጥና ሲያስተምር በፍጹም አይታይም። አብዛኛዎቻችን ውጭም ብንማርና ውጭ አገር አየሰራን ብንኖር፣ እስከተወሰነም ደረጃ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ እንድንማር ቀረጥ ከፍሎልናል። ትምህርት ቤት አስርቶልናል። ተምረንና አውቀን መልሰን እንድንረዳው፣ ከድንቁርናና ከድህነት እንድናላቅቀው ነው ይህንን ሁሉ ያደረገልን። ብሄራዊ ነፃነቷ የተከበረችና የሰለጠነች ኢትዮጵያን እንድንገነባለት ነው ይጠባበቅ የነበረው። ይህንን ከማድረግ ይልቅ ብቻውን እንዲጋፈጥ አድርገነዋል። ማንም እየመጣ እንዲጨፍርበት አድርገናል። ሳናውቀው ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ በቅተናል፤ አዋርደነዋልም።

በመሰረቱ ከአውሮፓ ምሁራን ብዙ ነገሮች በተማርን ነበር። በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ መንግስታት ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም፣ ቀዳሚውን ሚና የተጫወቱት ግለሰቦች ናቸው። ማንም ሳይገፋፋቸው በራሳቸው ጥረትና ውስጣዊ ግፊት የጥበብን ምስጢር በመፈለግ የግዴታ ህዝባችንን ከጨለማ ማውጣት አለብን በማለት የብርሃኑን መንገድ ያሳዩት ግለሰብ ምሁራን ናቸው። ከኩዛኑስ እስከ ዳንቴ፣ ከዳቪንቺ እስከ ሚካኤል ኤንጀሎ፣ ከኬፕለር እስከ ኒውተንና ላይብኒዝ፣ የኋላ ኋላም ሺለር፣ ጎተና ካንት፣ አንደዚሁም ብዙ የጥበብና የድራማ ሰዎች ብቅ ያሉትና ህብረተሰቦቻቸውን ለመለወጥ የተነሳሱት መንግስታት ስለቀሰቅሷቸውና ስላገዟቸው አልነበረም። የየግለስቦቹ ጥረት ነው። ጨለማንና ፊዩዳላዊ የድንቁርናን፣ አንዲሁም የካቶሊክን ጭፍን ሃይማኖት በመቃወም ነው በሳይንስ ላይ መረባረን የጀመሩት። የየግለሰቦችን ታሪክ ስንመረመር፣ አንዳንዶቹ የጻፉትን ሁሉ ለማሳተምና ለመበተን እየተቸገሩ፣ እንዲሁም እንዳይነቃባቸው እየተሰደዱ በመኖር የችግርን ፅዋ ይቀምሱ ነበር። በማያቋርጥ ትግል ግን በመጨረሻ ላይ ለአውሮፓ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለእኛም የሚተርፍ ሳይንስና ጥበብ ጥለውልን አልፈዋል። ዕውቀታቸው ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው አድርገዋል። ዘለዓለማዊ ነው። በህልማቸው ውስጥ ለአውሮፓ ብቻ ብለው አስበው የፈጠሩት ዕውቀት ሳይሆን፣ ከፍልስፍና እስከድራማ ድረስ ያለውን ግኝት ስንመለከት የሰውን ልጅ ባህርይ የሚመለከትና፣ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግኑኝነት ግንዛቤ ውስጥ ያገባ ነው። በመስረቱ የአውሮፓ የጥንቱ ዕውቀት፣ ታላቁ የሴኔጋል ሳይንቲስትና ፈላስፋ አንታይ ዲዮፕ እንደሚያስተምረን፣ ከግብጽ የተወሰደ ነው። ግሪኮች ይህንን በመውሰድ ነው ያስፋፉት። ከዚያም አውሮፓውያኖች የበለጠ ውስጠ-ኃይል በመስጠት ለካፒታሊዝም ዕድገት ይጠቀሙበታል። በሌላ አነጋገር ትግሉ ዕውቀታችንን መልሶ የማግኘት ትግል ነው።  ስለሆነም ወደ ኋላ ተመልሰን ታሪካችንን ማጥናት ይኖርብናል። ምናልባትም ለዛሬው ችግራችን መልስ ሊሰጠን ይችላል ብዩ እገምታለሁ።

እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል። ካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ ሳይንቲስቶች ያዳበሩትን በስምምነትና በስርዓት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር የሚኖረውን ስምምነት በመጣስ ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ወደ ተበዝባዥነት ለውጧቸዋል። የሰውም ልጅ ህይወት ሙሉ በሙሉ ማቴሪያላዊ እንዲሆን በማድረግ የሰው በሰው ግኑኝነት ወድ ንጹህ የገንዘብ ግኑኝነት እንዲለወጥ አድርጓል። በዚህም የተነሳ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የህሊና ቀውስና የአካባቢ መበላሸት እንዲደርስ አድርጓል። በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ጦርነት የጥሬ-ሀብትን ከመቆጣጠር ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የውክልና ጦርነቶች ናቸው። ስለዚህም ለህብረተሰብአችን ዕድገት በመንታገልበት ጊዜ ብዙ ነገሮችን ማውጣትና ማውረድ ይኖርብናል ማለት ነው። ምን ዐይነት የህብረተሰብ ሞዴል ነው ለአገራችን የሚያዋጣው እያልን ማጥናትና መከራከር ይኖርብናል። በአደገውም የካፒታሊስት ህብረተስብም ውስጥ አዲስ ሞዴልን ለመፈለግ ትግል እየተካሄደ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ካፒታሊዝም የሰው ልጅ ዕድገትና ስልጣኔ የመጨረሻው ቦታ ላይ አልደረሰም። ስለሆነም ካፒታሊዝም የመጨረሻው፣ የታሪክም መፈጸሚያው ላይ ነን ብለን ልናቆምና ነገረ ዓለሙን በሙሉ ልንተው አንችልም። ታሪክ ሂደት ነው። ክንዋኔ ነው። የሰው ልጅ አንድን ነገር እስኪያገኝ ድረስ ሳያቋርጥ ይፈልጋል። ህይወታችንና የሰው ልጅ ታሪክ እንደ ወንዝ ውሃ ፈሳሽ ናቸው። ከዚህ ስንነሳ የህብረተሳብችን የወደፊት ዕጣ ምን ይመስላል? ለመጭው ትውልድስ ምን ጥለንለት ነው ማለፍ ያለብንና? የምንችለው? ብለን ማውጣትና ማውረድ ይኖርብናል።

በእርግጥ አሁን በአለው እጅግ የተወሳሰበና ግራ የሚያጋባ ዓለም የየአገሮችን የወደፊት ዕድል መወሰን ያስቸግራል። ሁሉም ነገር ከገበያ አንፃር በሚታሰብበት ዓለም ስልጣኔና የሰው ልጅ ትርጉም እያጡ መጥተዋል። የየአገሮች ዕድገት መለኪያ ንግድና ብዙ ትርፍ ማካበት ሆነዋል። ውብ ውብ ከተማዎች፣ ጥበብና ድራማ፣ ለሰው ልጅ የሚስማሙና፣ ከአካባቢውና ከአየሩ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ የቤት አሰራሮች ከረዥም ጊዜ አንፃር ታስበው አይሰሩም። በእኛ አገርና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለው ከፍተኛ ምሁራዊ ክፍተት ኢንቬስተር ነን የሚሉት እንደፈለጋቸው እየገቡ እንዲፈተፍቱ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰፊው ህዝብ በአገሩና ለሀብቱ ባይተዋር በመሆን፣ እንዲሁም ደግሞ በፍርሃት በመዋጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። አገሮችና ህዝብ ታሪክ የሚሰራባቸውን የሚሰሩ መሆናቸው ቀርቶ ጥቂት አዋቂ ነን ባዮች ውስጥ ካለው ኃይል ጋር የእጅና ጓንቲ በመሆን አገር እያፈራረሱ ነው። ይህንን ዐይን ያወጣና ታሪከ-ቢስ ተግባር የሚቃወሙ ደግሞ አናርኪስቶችና አሸባሪዎች ወይም ግራዎች አየተባሉ ይወነጀላሉ። ይህን ሁሉ የሚመለከተው ነገሩን ባለመረዳት ዝም ብሎ “ሌሎች ሲዘርፉ እኔም አብሬ ልዝረፍ“ በማለት አብሮ አገር ያወድማል፤ ታሪክ ያበላሻል። ይህንን ዐይነቱን እጅግ የዘገነነ ሁኔታ እስከመቼ ድረስ ነው ውጦ የሚተኛው?  በካፒታሊስት አገሮችም ኢንቬስተሮች ነን የሚሉ ብዙ ነገሮችን እየተቆጣጠሩና እያበላሹ መጥተዋል። ይህንን አስመልክቶ ሰሞኑን እዚህ የምኖርበት ከተማ ውስጥ የቀኝ ኮንሰርቫቲቦች፣ ዘ ወርልድ የሚባለው ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ፣ ስለቤት አዲስ  የአሰራር ባህል ላይ ሰፊ ዘገባ ቀርቧል። በትንተናው መሰረት ባለፉት ሰላሳ ዐመታት ከንጹህ የኢኮኖሚና የትርፍ አንጻር ብቻ ታስበው የሚሰሩ ቤቶች የየከተማዎችን ስዕሎች እንደቀየሯቸውና፣ በሰው የህሊና አወቃቀር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር እንደቻሉ ይዘግባል። ከማዕከለኛው ዘመን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው የመኖሪያ ቤቶች አሰራር፣ ሱቆችና ትላልቅ የመንግስታት ህንጻዎች ጋር ያወዳድራል። በመሆኑም ይላል፣ የሚሰሩት አዳዲስ ህንጻዎች በሙሉ የተወሰነ የጂኦሜትሪን ቅርጽ የማይከተሉና ሀርሞኒየስ ባህርይ የሌላችውና እንዲሁም ዘላቂነት እንደሌላቸ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። በሌላ ወገን ደግሞ በጥንቱ ዘመን መኖር፣ ዕውቀት መቅሰም፣ ባህላዊ ክንዋኔዎች፣ መጻህፍት ቤቶች፣ የሚያማምሩ ቡና ቤቶች ወዘተ… አንድ ላይ ሆነው የሚገነቡ ነበሩ በማለት ትዝታ ውስጥ ይከተናል። ትላልቅ ግቢዎች፣ ሰፊ ጓሮ ሲኖራቸው  ኗሪውን የሚያገናኙ ነበሩ። የዛሬው የህንፃ አሰራር ከኢኮኖሚ አንጻር ብቻ የሚሰራ በመሆኑ የከተማዎችን ውበት እያበላሸና የህዝቡን የማሰብ ኃይል እያዘበራረቀው ነው በማለት ያለውን ቅሬታ ያስቀምጣል። ይህም የሚያመለክተው ዕድገትንና አጠቃላይ የሆነን የኑሮ ስልት በሚመለከት አሁንም ውይይት ይካሄዳል። ጥቂት አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች በአንድ አገር ላይ መወሰን እንደሌለባቸው ያመልክታል። ይህ ዐይነቱ ክርክር ከኢኖሚክስ አንስቶ እስከትምህርትና፣ እስከሌሎችም ድረስ የሚዘልቅ ነው። ጥቂት ኤሊት ነኝ በሚለው፣ በኤንቨስተሮችና በህዝቡና ሰፊ ምሁራዊ ዕውቀት ባላቸው ዘንድ የጦፈ ክርክር ይካሄዳል።

ያም ሆነ ይህ  ለዕድገት የሚደረገው ትግል እስቸጋሪ ነው። ምሁራዊ የሆነ ግልጽ ውይይት በማይካሄድበት በእንደኛ ባለ አገር ውስጥ የዕድገትን ሂደትና ዓለምን በሁለት አማራጮች ብቻ ወስኖ ማውራት የተለመደ ሆኗል። ይኸውም በገበያ ኢኮኖሚና በሶሻሊዝም መሀከል የሚደረግ ትግል ነው የሚል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ስለገበያ ኢኮኖሚ ያለው አመለካከት ግልጽ በሆነ መልክ ተተንቶኖ አይቀርብም። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የገበያ ኢኮኖሚ የሚለው ግዙፍ አባባል ከንግድ ጋር ብቻ ተያይዞ ነው የሚታየው። ይህም ማለት በንግድ ላይ በሚመረኮዝ፣ ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮች እንደሚታየው የገበያ ኢኮኖሚ እየተባለ በሚወራውና በንጹህ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ላይ ያለው ግንዛቤ ግልጽ  አይደለም። አብዛኛው የትኛውን እንደሚፈልግ አይነግረንም፤ መንገዱንም አያሳየንም።

ይህንን ውዝንብር ትተን ከላይ ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደመኮርኩት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ የወደፊት ዕርምጃና የሚያዋጣውን ነገር ለመጠቆም ከንጹህ የኢኮኖሚ ስሌት ብቻ መነሳቱ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው። መነሳት ያለብንና መንደፍም ያለብን ዕቅድ ጠቅላላውን ኢትዮጵያ እንደ ብሄራዊ፣ እንደሀብረተሰብአዊ፣ እንደማሀበራዊ፣ እንደባህልና እንደስነምግባራዊ ፕሮጀክት በመውሰድ ብቻ ነው። በዚህ ዐይነቱ ስፊ ፕሮጀክት ውስጥ ለግለሰብአዊ መብት፣ ለነጻ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ በህብረት ለሚካሄድና በመንግስት በሚደገፍ እያለን እየነጣጠልን ማስቀመጥ እንችላለን። የገበያ ኢኮኖሚ የሚለውም ፅንሰ-ሃስብ በዚህ የሚጠቃለል ሲሆን፣ ዋና አንቀሳቃሽ ሃይል ማኑፋክቱር ነው። የትናንሽና የማዕከልኛ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የዕደ-ጥበብ ሙያዎች የሚስፋፉበት ይሆናል። ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚዊ ክንዋኔና አንቅስቃሴ ወደ ካፒታሊዝም ያምራ አያምራ ከዛሬውኑ ልንወስን አንችልም። የዛሬውን ህልማችንና ጅማሮአችንን አዳዲስ ኃይሎች በመምጣት ሊያፈራሱት ይችላሉ። ከሞትን በኋላ መቃብር ውስጥ ሆነን ምን እንደሚሰሩ ልናያቸውና ልንቆጣጠራቸው አንችልም። በሌላ ወገን ግን ከብዙ አገሮች ልምድ መማር እንደሚቻለው፣ አንድ እንደባህል የተወሰደ አሰራርና ሰፋ ያለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ያለው ህብረተሰብ ማንም እየመጣ የሚጨፍርበት አገር አይሆንም። ብዙ የሚያበላሹ ነገሮችና ኃይሎችን በምሁራዊ ኃይልና ክርክር መግታት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ ሰፋ ያለ የሲቪል ህብረተሰብ መቋቋም አለበት። በዚህ አማካይነት ብቻና፣ ህበረተሰብአዊ ባህርይ ያለው ኢንስቲቱሽንና አገዛዝ ከተመሰረተ የህብረተሰብአችን የዕድገት ጉዞ የተቃና ይሆናል።  መልካም ንባብ!

fekadubekele@gmx.de

 

ማሳሰቢያ፤ በዚህ መልክ ወደ ፊት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲቀርብ ለሚፈልጉና አገርቤትም ይህ ዐይነቱ ጥናትና ምርምር በተቋም ደረጃ እንዲስፋፋ ከተፈለገ የግዴታ ሰፋ ያለ የማቴሪያል ድጋፍ ያስፈልጋል። እንደዚህ ዐይነቱ ጥናትና ምርምር በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ ሊወድቅ አይችልም። በጣም አድካሚና የራስን ሀብት የሚጨርስ ነው። የግዴታ ተባብሮና ተደጋግፎ መስራት ያስፈልጋል።

 

AFRICA  DEVELOPMENT                                      

CONSULTING

 

 ADC  Dr. Fekadu Bekele

E-Mail: fekadubekele@gmx.de

Bank: Berliner Sparkasse. IBAN: DE13 1005 0000 032 032 5539

HOLISTIC MODEL-AFRICAN RENAISSANCE

  • Resource Based Development &Human Power
  • Organic Growth/ from bottom upwards
  • Science & Technology/Innovation
  • Entrepreneurship
  • Finance & Money
  • Institution/The Role of Government
  • Environment & Social