[gtranslate]

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!

                                                                                                                                                                                             ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                                                                                                                           ግንቦት 19 2016(ግንቦት 27 2024)

መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት” ብሎ ከሚጠራው፣ በአሁኑ ወቅት አሜሪካን በስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ከሚሰራ፣ በመጀመሪያ ደረጃ የራሱን ሰፋ ያለ ዘገባ ከሰጠ በኋላ ቶፕ ዲፕሎማት ብሎ የሚጠራውን ኢትዮጵያዊ አሜሪካን ከኢትዮጵያ ጋር ስላላት ግኑኘነትና ከኢትዮጵያ መንግስትም ስለምትጠብቀው ነገር በመጠየቅ አዳማጩን “አዲስ የፖለቲካ ትንተና” የሆነ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ አስተሳሰብን አስተምረውናል። ይሁንና ግን የመሳይ መኮንንም ሆነ “የከፍተኛ ዲፕሎማቱ” ዘገባና የጥያቄ መልስ በኢምፔሪካል በሚደገፍ ዕውነተኛ ሳይንሳዊ መለኪያ ውድቅ ነው። ሁለቱም ያቀረቡት ትንተና ከተጨባጩ የአገራችን ሁኔታና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም አቀፍን ህግ እየጣሰ አልታዘዝ ያሉትን ነፃ አገሮች በአውሮፕላንም ሆነ የምድረኛ ጦር በመላክ ከሚያካሂደው የማንአለብኝነት የማውደም ተግባሩ ጋር የሚሄድ አይደለም። ይህ ብቻ ሳይሆን ይወዳደሩኛል የሚላቸውን አገሮች በተዘዋዋሪ አጎራባች አገሮችን “አጋሩ” በመሰረቱ ታዛዡ በማድረግ የውክልና ጦርነት እንዲካሄድ ከሚያደርገው የአንድን አገር ሰላም ብቻ ሳይሆነ የአንድ አካባቢን ሁኔታ ከሚያደፈርሰው የተዘዋዋሪም ሆነ የቀጥታ ጣልቃ-ገብ “ፖለቲካው” ጋር ሲነፃፀር መሳይ መኮንንም ሆነ “ቶፕ ዲፕሎማት” ብሎ የሚጠራው የአሜሪካ ተላላኪ የሆነው ኢትዮጵያዊ የሰጡት ዘገባና የጥያቄ ምልልስ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም።

በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን የመሳይ መኮንና የጠየቀውን ሰው ሙሉ ዘገባና መልስ ካዳመጥኩኝ በኋላ በኋትስ አፔ ላይ የቋጠርኩት የመሳይ ቪዲዮ ምክንያቱ በማይታወቅ ነገር ተሰርዟል። በምትኩ እሱ ከሰጠው ጋር የማይገናኝ ሌላ ቪዲዮ በመተካት፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከበስሩ የሰጠኹት ትችት እንዳለ ተቀምጧል። ቪዲዮውም ስለተሰረዘ ወይም እንዲጠፋ ስለተደረገ-ምናልባት በራሱ በመሳይ መኮንን ሊሆን ይችላል፣ የጠቀሰውን “የከፍተኛ ዲፕሎማት”  ብሎ የጠራውን ሰው  ስም ስላልመዘገብኩ እከሌ ነው ብዬ ስሙን እየጠቀስኩኝ ለመጻፍ አልቻልኩም።

ወደ ቁም ነገሩ ስመጣ የቀድሞው የኢሳት ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅና ጋዜጠኛ፣ በአሁኑ ወቅት የአንከር ሚዲያ ባለቤት የሆነው መሳይ መኮንን  የአገራችን ጠ/ሚኒስተር  የሆነው አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዳታለለ ሁሉ አሜሪካንና የተቀረውንም  የምዕራቡን ካፒታሊስት ዓለም እንዳታለለ አብስሮልናል። ስለሆነም ይለናል መሳይ መኮንን፣ የአሜሪካን መንግስት በአቢይ አህመድ ፖለቲካና በህዝባችን ላይ ስለሚፈጽመው የሰብአዊ መብት ገፈፋ ስላልተደሰተ ከስልጣን የሚወገድበትን መንገድ እየፈላለጉ ነው ይለናል። በመሳይ መኮንን ዕምነት አቢይ አህመድ አሜሪካኖችን በማስፈራራት የሚያካሂደው ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውንም የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ሊያናጋ ይችላል ብለው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ይህም ማለት በባይደን የሚመራው የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያስብና፣ ሁኔታውም በዚህ መቀጠል የለበትም ብሎ እንደተነሳ መሳይ መኮንን ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የፖለቲካ ስሌት ጋር ሊጣጣም የማይችል አዲስ ዐይነት የሆነ  የፖለቲካ ትንተና ያስተምረናል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ሲወጣ በዚያን ጊዜ ለኢትዮጵያም ህዝብ ሆነ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም “በዚህ መልክ ነው በኢትዮጵያ ምድር ፖለቲካ የማካሂደው” ብሎ በምን መልክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል-ኪዳን እንደገባና አሜሪካንንም ሆነ የተቀረውን የምዕራቡን ካፒታሊስት ዓለም እንዳሳመነ መሳይ መኮንንም ሆነ ቶፕ ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት በፍጹም ሊያስረዱን አልቻሉም። እንዲያው ብቻ አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዳታለለ ሁሉ የአሜሪካንንም አታሏል ይለናል። ስለሆነም አቢይ አህመድ በሚያካሂደው መሰረተ-ሃሳቡም ሆነ ዋና ዓላማው በማይታወቅ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን እንዳለ የምትናጋው፣ በአጠቃላይም በአካባቢው ከቁጥጥር ውጭ የሚሆን አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም እንዳለባቸው አቶ መሳይ መኮንን አብስሮልናል። መሳይ መኮንን ሊነግረን የፈለገውና ሊያሳምነም የሞከረው አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ለዓለም ህዝብ ሰላም፣ ደህንነትና ብልጽግና እንደሚታገሉና እንደቆሙ መሰረታዊ እሴታቸውም(Core Values) እነዚህ እንደሆኑ ነው። አዲስ የፖለቲካ ቲዎሪና ሳይንስ ነው የምንማረው ማለት ነው።

የመሳይ መኮንና የቶፕ ዲፕሎማቱን የተሳሳተ ዕምነትና ዘገባ በሚገባ ለመረዳት አንዳንድ መሰረታዊ ጎዳዮችን እንጠቅስ። በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን የአንድ አገር የውስጥ ፖለቲካም ሆነ የዓለም ፖለቲካ ብለው የሚጠሩት ነገር እንደዚህ ነው፣ እንደዚህ ብለው ያስባሉ፣ ወይም ደግሞ የዓለም ፖለቲካ በወዳጅነትና በጠላትነት ላይ በመመስረት  የሚካሄድ ነው እያሉ የሚነገር ወይም ለመተንተን የሚሞከር ሳይሆን ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማንበብና የዓለም ዋናው ተዋናይ ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩና ይህም አስተሳሰባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚታገሉ እንደ አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮች የራሳቸውን የበላይነት(Hegemony) በሁሉም አገሮች ለማስፈን ከሚታገሉት ኃይሎች ብቻ በመነሳት ነው፤ ተጨባጭ ሁኔታዎችንን በማንበብና ፖለቲከኞች ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩትን ሰዎች አካሄዳቸውንና ፖሊሲያቸውንም መገምገም የሚቻለው። እንደሰለጠንበትና እንደፖለቲካ ዕምነታችንም አንዳች ዐይነት ሀታተ ለመስጠት የምንችለው በአቦ ሰጡኝ ሳይሆን አንዳችን ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍናን መሰረት በማድረግ ብቻ ነው። ስለሆነም በተለይም አንድ ኃይላን መንግስት ነኝ የሚል አገር እመራዋለሁ ብሎ የሚጠራውን ህዝብ ጥቅም በማስጠበቅ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖለቲካን የሚያካሄደው በአገሩ ውስጥ የሰፈነውን የኃይል አሰላለፍ መሰረት በማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በተለይም የአሜሪካ የውጭ ፖለቲካ በሲአይኤና በሌሎች ወደ አስራስምንት በሚጠጉ የስለላ ድርጅቶች የሚደገፍ ሲሆን፣ የሚተገበረውም በፔንታጎን ነው። ይህም ማለት ስልጣንን የያዘውና በግልጽ የሚታየው ፕሬዚደንት አይደለም የአሜሪካንን የውጭ ፖለቲካ የሚደነግገው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ አሜሪካ የሚያካሂድው የውጭ ፖለቲካ ይህንንም ሆነ ያንን አገር ለመጥቀምና ወደ ውስጥ ደግሞ የተስተካከለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና አንድ ህዝብ በሰላምና በደስታ እንዲኖር ማድረግ ሳይሆን ታዛዥ ኃይልን በመፍጠርና ጭንቅላቱን በመስለብ ስልጣን ላይ በማውጣት እነሱ በሚፈልጉት መልክ የአንድን አገር ፖለቲካ ማተረማመስና ህዝቡም አቅጣጫውን እንዲያጣና በራሱም ላይ እንዳይተማመን ማድረግ ነው። በዚያው መጠንም የአንድን አገር እሴት እንዳለ በማፈራረስ ሀብቱን መዝረፍና ማዘረፍ ነው። ይህ ነው የአሜሪካን ዋናው የውጭ ፖለቲካ መመሪያው።

ላይ ከሰጠሁት አጠር መጠን ካለ ማብራሪያ ስነሳ የዛሬ ሰላሳ ስድስት(36) ዓመት ገደማ፣ ማለትም ወያኔ በአሜሪካንና በእንግሊዝ እምፔሪያሊዝም በመታገዝ ወይም በመደገፍ በአውሮፓ አቆጣጠር በ1991 ዓ.ም ስልጣን ላይ ሲወጣ ዋናው ዓላማውም የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ እንዲነደፍ በማድረግ በአገራችን ምድር ጠቅላላውን ህዝብና አገራችንን እንደ ህብረ-ብሄር የሚመለከትና የሚያጠነክር ፖለቲካ እንዳይካሄድ ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የጎሳ ፌዴራሊዝም ብለው የሚጠሩትን፣ እነሱ በመብትና ነፃነትን በማክበር ስም፣ ይሁንና ደግሞ የእያንዳንዱን ጎሳ መብት የማያስጠብቅና ዕውነተኛ ነፃነትን እንዳይጎናጸፍ የሚያደርግ ፖለቲካ ብለው የሚጠሩትን ነገር ተግባራዊ እንዲደረግ በመገፋፋት ነው ህዝባችንና አገራችንን የሚያዳክምና በቀላሉ መቋጫ የሌለው ውዝግብ እንዲፈጠር መንገዱን ሁሉ ያመቻቹት። ወያኔም ስልጣን ላይ ሲወጣ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከተቀረው የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ነፃ የሆነ የአገራችንን ህዝብ በአንድነት ተነሳስቶ በመንቃትና በመደራጀት አገሩን እንዲገነባና ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት የሚላቀቅበትን ፖለቲካ ማካሄድ ሳይሆን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ታዛዥ በመሆን አገርን ከውስጥ እንዲቦረቦር ማድረግ ነው። ስለሆነም የሪፓብሊካንና ዕውነተኛ የሆነ የግለሰብ ነፃነትን የሚያውጀውንና ተግባራዊም መሆን የሚገባውን አንድን አገር በአስተማማማኝ መሰረት ለማስገነባት የሚያስችለውን ፖለቲካ ከማካሄድ ይልቅ ይህንን መሰረተ-ሃሳብ የሚፃረረውን የጎሳ ፌዴራሊዝም በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንዲሆን መገፋፋት ዋና ዓላማው አንድን አገር ከማዳከምና በዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ ዘፍቃ እንድትኖር ከማድረግ ውጭ የሚታሰብ አይደለም። በዚህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝምና በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲስፖታዊ አገዛዝን ማስፈን የሚቻለው። ይህም አካሄድ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ በህግ ላይ የተመሰረተ ስርዓት(Rules based system) ብለው ከሚጠሩት ጋር የሚጣጣምና የየአገሮችን ነፃነት ሳይሆን የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረውን የምዕራቡን ካፒታሊስት ዓለም የበላይነት የሚያፀድቅና አምነንም እንንነቀበለው የሚያደርግ ነው። ይህ ዐይነቱ ስርዓትም በመሰረቱ የኢንላይተንሜትን ወይም የሊበራሊዝምን አስተሳሰብ እንዳለ የሚፀረር በመሆኑ ዘመናዊ የሆነ ፊዩዳላዊ አገዛዝ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

በጎሳ ፌዴራሊዝም ስም የሚተገበረው የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ ደግሞ የግዴታ የአንድን አገር የጥሬ-ሀብት የሚያስበዘብዝ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ በመደገፍ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ በሚያደርገው የኒዎ-ሊበራል “የኢኮኖሚ ፖሊሲ” መደገፍ አለበት። የኒዎ-ሊበራሊዝም መሰረታዊ አስተሳሰብ ደግሞ የነፃ ንግድ ሲሆን፣ ሁሉም አገር ገበያውን ከውጭ ለሚመጣ የፍጆታ ዕቃና ግልጋሎት ክፍት ማድረግ አለበት። በሌላ አነጋገር የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ከማሟላትና ህዝብን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ ማንኛውም ነገር በገበያ ህግ ብለው በሚጠሩት መተዳደር አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም አገዛዝና ህዝብ ከራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም በመነሳት ከታች ወደ ላይ በዕውቅና በዕቅድ በመገንባት ራሳቸውን ነፃ ማውጣትና ራሳቸውን መቻል ሳይሆን ሁሉም ነገር ለገበያው ተዋናይ ኃይሎች መተው አለበት፤ በዚህም አማካይነት ነው በአሃዝ የሚለካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው ይሉናል። ይህም ማለት ዐይነታዊና መስረታዊ ለውጥ ሳይሆን የአንድ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ዓላማ በአሃዝ የሚለካ የኢኮኖሚ ዕድገት  ባቻ ነው።  ሀቁ ግን ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ከጥቂት ግዜያት በኋላ በነፃ ንግድና ገበያ ተግባራዊ ያደረገው “የኢኮኖሚ ፖሊሲ” የአገራችንን ሀብት እንዲዘርፍ ነው አመቺ ሁኔታን የፈጠረለት። የወያኔ ካድሬዎችም ሳይሰሩ፣ ሳይፈጥሩና የማውዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ሳያካሂዱ ነው በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሀብት ሊደልቡና ለመባለግም የቻሉት። ይህ ድርጊታቸውም በመሰረቱ የካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ክንዋኔን ህግ የሚጥስ ነው። ደረጃ በደረጃ መካሄድ የሚገባውን የመዋዕለ.-ነዋይ ሂደት የሚፃረር ነው። የቴክኖሎጂ ውድድር እንዳይደረግና፣ ገበያውም በስፋትም ሆነ በጥራት እንዳያድግ የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው። ይህ ዐይነቱ የገበያ ክንዋኔም ዞሮ ዞሮ ለዘራፊዎችና ለአጭበርባሪዎች የሚያመች ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን፣ በዚያው መጠንም ደካማውን ወይም አቅም የሌለውን አስፈንጥሮ በመጣል ከቆሻሻ መጣያ ምግብን እየፈለገ እንዲመገብ የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይህ ነው በወያኔ የ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመን በነፃ ንግድና በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ ለመሆን የበቃውና አገራችንና ህዝባችን እንዲዳከሙ ያደረገው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታም ነው ለፖለቲካ ውዝግባና ለትርምስ አመቺ ሁኔታን የፈጠረው። ምክንያቱም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የሚደገፍ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሌላት አገር ዕጣዋ ዘለዓለማዊ ውዝግብና ህዝቦቿም በድህነት ዓለም ውስጥ የሚገኙና የሚኖሩ ሰለሚሆን ነው።

አጠቃላዩን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የህወሃት አገዛዝ ወይም ወያኔ ጠቅላላውን የፖለቲካ መድረክ በመቆጣጠር አጠቃላይ የሆነ ጭቆናን ለማስፈን ችሏል። የሰብአዊ መብት ጥስት በከፍተኛ ደረጃ ሊካሂድ ችሏል። ከጥቂት ጊዜ በስተቀር በነፃ ሃሳብን መግለጽና ሰላማዊ ሰልፍም ለማድረግ እንዳይቻል ተደርጓል። በአጠቃላይ ሲታይ የህግ የበላይነት የተጣሰበትና አንድ ጎሳ  የፖለቲካውን መድረክ የሚቆጣጠርበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ስለሆነም በዚህ ዐይነት የውንብድና ፖለቲካ ራሱን በፖለቲካ አስተሳሰብ አዳብሮ ሊወጣ የሚችል ኃይል ሊፈጠር አልቻለም። ሰፊውም ህዝብ እንዳይነቃ በመደረጉ ለመበቱ ለመታገል የሚያስችለውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በየቦታው መመስረት አልቻለም። በአጭሩ ማለት የሚቻለው ኢትዮጵያ በህወሃት የአገዛዝ ዘመን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም በመታገዝ የኋሊት ጉዞ እንድታደረግ ነው የተረገመችው። አሁንም በሌላ አነጋገር፣ የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ወያኔን ስልጣን ላይ ሲያወጡ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሰብ ሳይሆን እንደዚህ ዐይነቱን በአስተሳሰቡ ወደ ኋላ የቀረና የቀጨጨ ኃይልን በመጠቀም ጠቅላላውን አገራችንን መበወዝና ሰፊውን ህዝባችንንም አቅመ-ቢስ ማድረግ ነው። ይህ ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ብሄራዊ ጥቅም። አንድን አገር በፀና መሰረት ላይ መገንባት ሳይሆን በዘለዓለማዊ ውዝግብ ላይ እንድትኖር ማድረግ ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ዋናው የውጭ ፖለቲካ የብሄራዊ ጥቅም መመሪያ።

ወያኔ 27 ዓመት ያህል እንደሎሚ ከተሟጠጠ በኋላ በዚያ የማወናበድ ፖለቲካው ሊቀጥል አልቻለም። ለሰፊው ህዝብ አስተማማኝ ሁኔታ የማይፈጥር አገዛዝ በሽወዳና በከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ ብቻ ወደፊት ሊጓዝ አይችለም። የፖለቲካ መሰረተ-ሃሳብም ሽወዳና አንድን ህዝብ ከፋፍሎ በመግዛት አቅሙን ማዳከም ሳይሆን የሚያጠነክረውን ጥበባዊ ፖለቲካ ማካሄድ ነው። ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መሰረት ወደ ሽዋጅነት የሚለወጥ ፖለቲካ የግዴታ የአንድን አገር ችግር ውስብስብ ያደርገዋል። ችግሩም እየተባባሰ ሲሄድ ራሱ አገዛዙ በፈጠረው ችግር ውስጥ በመውደቅ መንደፋደፍ ይጀምራል። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎችንም ችግሮች ከሳይንስ አንፃር ሊፈታ የማይችል አገዛዝ ለዝንተ-ዓለም በስልጣን ላይ ሊቆይ አይችልም። ስለሆነም ወያኔ ራሱ ባጠመደው ውጥመድ ውስጥ በመግባት ነው መንደፋደፍ የጀመረው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው አማራጭና ዘላቂነት ያለው ሳይንሳዊ መፍትሄ መስጠት ሳይሆን፣ ወያኔን ከገባበት ወጥመድ በማላቀቅና አሽቀንጥሮ በመጣል ችግሩን በሚያባብስ ሌላ ጭንቅላቱ በተበወዘና በቀጨጨ ኃይል መተካት አለበት። ለዚህ ደግሞ አቢይ አህመድ በጣም አመቺ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አቢይ አህመድ ወያኔ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረውን አገርን የሚያፈራርስና ህዝብን የሚያደኸይ ፖለቲካ ለማረም የተነሳና መንፈሱም በጥሩ አስተሳሰብ የታነፀ አይደለም። ስለሆነም በአዲስ ፍልስፍናና ሳይንስ በመመራት ሁለ-ገብ ፖለቲካና ፖሊሲ ማካሄድ የሚችል ሳይሆን የነበረውን ፖለቲካዊ ውዝግብ፣ ኢኮኖሚያዊ ድክመትና የማህበራዊ መጎሳቆል ማባባስና ጥልቀትም እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህንን ሁኔታ እኛ ባይገባንም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ጠንቅቀው ያውቃሉ። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መንፈሳቸው በታነፀና በዳበረ ኃይሎች የተያዘና ፖለቲካውም በሳይንስና በፍልስፍና ላይ በመመርኮዝ የሚመራ ስላልነበር ራሳቸውን ተገዢና ታዛዥ ለመሆን ለሚፈልጉ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ስልጣን ለመያዝ የሚያመች ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ተኳኩለውና ሱፍ ለብሰው ራሳቸውን እያታለሉ ስልጣን ላይ ለመውጣትና ለመታዘዝ ለሚፈልጉና፣ በፖለቲካም ስም ለሚነግዱ ቡድኖች  የአገራችን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላውም የአፍሪካ የፖለቲካ መድረክ አመቺ ሆኖ የተዘጋጀ ይመስላል። በተለያየ ጊዜያት ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሆነ ፖለቲካ ያካሂዱ ስለነበርና፣ ስለሚያካሂዱም የግዴታ አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ ከመገንባትና የህዝብ አለኝታ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ ማንም እየተነሳ የሚጨፍርበት መድረክ ሳያውቁት ለመፍጠር ችለዋል።

ስለሆነም አቢይ አህመድና ተከታዮቹ ስልጣን ላይ ሲወጡ ሳቃቸውንና መልካቸውን ከማየታችን በስተቀር በዚህ መልክና ፍልስፍና ነው አገራችንን ወደፊት ልናራምዳት የምንችለው ብለው የነገሩን ነገር አልነበረም። እንዲያው ብቻ በአቢይ አህመድና በመልኩ በመሸወድ በአገራችን ምድር ሊበራል የሆነ አገዛዝ የሚሰፍን መስሎንም ነበር። ሀቁን ለመናገር ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው በተለይም በፖለቲካው ውስጥ እሳተፋለሁ የሚለው ምሁርና የፖለቲካ ኤሊት ነኝ ባይ ተሸውዷል ማለት ይቻላል። የፖለቲካ ፍልስፋናና ጥበብ በማይታወቅበት፣ ትንተና በማይሰጥበትና አዳዲስ አስተሳሰቦችን ለማፍለቅ በማይቻልበት አገር ውስጥና ልማድም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ አንድን ሰው ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ህዝብ እንዳለ መሸወድ ይቻላል። በተለይም በአለፉት ሃምሳ ዓመታት የፖለቲካ ቲዎሪንና የፖለቲካ ፍልስፍናን አስመልክቶ ምንም ነገር ስላልተሰራ መከራከሪያና መተንተኛ ዘዴ በፍጹም የለም ማለት ይቻላል። ስለሆነም ሁላችንም መሸወዳችን የሚያሰደነቅን ሊሆን አይገባውም።

አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣና ትንሽ ጊዜ ያህል ከተንገዳገደ በኋላ አደገኛ ናቸው የሚላቸውን ኃይሎች ሰበቦችን እየፈጠረ ነው ካለበቂ ምክንያት እንዲገደሉ ያደረገው። በተለይም በአማራው ክልል አንዳንድ የክሉሉን መሪዎች ለመግደል የበቃው ስልጣኔን ይቀንቀኑኛል፣ ወይም እንቅፋት ይፈጥሩብኛል ብሎ ያሰባቸውን ኃይሎች በጠራራ ፀሀይ ላይ በማስገደል ነው የፖለቲካ መድረኩን ወደመቆጣጠር ያመራው። ይህ ዐይነቱ አደገኛ አካሄዱ ደግሞ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምዕመናን ላይ በመስፋፋት ምዕመናን ሊገደሉ፣ ሊሳደዱና ሊደበደቡ በቅተዋል። በሌላ አነጋገር፣ ሊበራል ነው ተብሎ የተገመተው  ወይም የታሰበው ሰው የሰይፍ መርዙን ነው መምዘዝና ተቀናቃኝ ይሆኑኛል ያላቸውን ግለሰቦች በሙሉ መግደልና ማሳደድ የጀመረው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ በማንኛውም የፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና እንዲሁም ሳይንስ የሚደገፍ አይደለም። መላ ቅጥ የሌለውና ለራስም ሆነ እወክለዋለሁ የሚለውን ብሄረሰብ የሚበጅና ነፃ የሚያወጣውም አይደለም። በአጭሩ ለጊዜውም ቢሆን የአቢይ ፖለቲካ የሽወዳ ፖለቲካ ቢመስልም ገጽታው ላይ የተጋረደው ሽፋን ሲገለጥ ዕውነተኛ ማንነቱን ማጋለጥ ችሏል፤ ጭራቅነቱን አረጋግጧል። ሰው ሳይሆን ነብር ወይን አንበሳ ነው ወደ መሆን ያመራው። ነብርና አንበሳ እንኳ እንድ ጊዜ የሚፈልጉትን ነገር ካገኙ በኋላ ሲጠግቡ ተንጋለው ይታኛሉ። የአቢይ አህመድ ወደ አውሬነት መለወጥ ግን በቀላሉ የሚያጠግበው አይደለም። በደመ ነፍስ በመመራት የሚያደርገውን የሚያውቅ አይደለም። ይህ ዐይነቱ በየዕለቱ ግልጽ የሆነው አደገኛ አካሄዱ ቀስ ቀስ እያለ ለእኛ ግልጽ ነው ሊሆን የቻለው። አንዳንዶች ደግሞ አሁንም አምርረው በአቢይ የሚያምኑና የሚያመልኩ አሉ። እዚህ የውጭ አገር የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩና የህግ የበላይነትንም እየኖሩበት አሁንም ቢሆን አቢይ አህመድን አምነዋለሁ የሚሉ አሉ።  በሌላ ወገን ግን አሜሪካኖችና ግብረ-አበሮቹ  እንደዚህ ዐይነቱን ኃይል ስልጣን ላይ ሲያውጡ ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንዳማይችል በሚገባ ያውቃሉ። ስለሆነም መሳይ መኮንን አቢይ አህመድ አሜሪካኖችን አታሏል የሚለው በኢምፔሪካል ሳይንስ ወይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከሚያካሄደው የሰባ አምስት ዐመት አገሮችን የማዳከምና የግድያ ፖለቲካ የሚረጋገጥ አይደለም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነትን ከተቀዳጀ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ ከሂሮሺማ እስከናጋሳኪ፤ ኮሪያና  ቬትናም፣ በቅርቡ ደግሞ ኢራቅ፣ ሊቢያና አፍጋኒስታን ድረስ ማንነቱን አጋልጧል። ሰበቦችን እየፈለገ ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ የሚያስቆጥሩና ለምዕራቡ ስልጣኔም የሚሆን መሰረት የጣሉና ታሪክም የነበራቸውን እንደነ ኢራቅ የመሳሰሉ አገሮችን አውድሟል። ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ገድሏል። የታሪክ ቅርሳቸውም እንዲወድምና እንዲዘረፍ አድርጓል። ስለሆነም አሜሪካን አገሮችን ከማውደም በስተቀር የሚገዛበት እሴት የለውም። ብሄራዊ ጥቅሙም አገሮችን በማውደምና ሀብታቸውን በመዝረፍ ብቻ ነው ሊጠበቅ የሚችለው ብሎ የሚያምነው።

ከዚህ ሀቅ ስንሰሳ አሜሪካን ለኢትዮጵያ ያሰበችበትና ለዕድገቷም አመቺን ሁኔታ የፈጠረችበት ጊዜ አልነበረም‹፣ የለምም። አሜሪካን አፄ ኃይለስላሴ ስልጣንን እንደገና ሲይዙ የጠበቀ ግኑኝነት ለመፈጠር የበቃችው በአካባቢው ግርማ ሞገስና በኮሙኒዝም ስም ተሳቦ ሊመጣ የሚችልን ዕድገት ሊያጨናግፉ ይችላሉ ብሎ በማሰቡ ብቻ ነው። አሜሪካ ለኢትዮጵያ ቢያስብ ኖሮ ኢትዮጵያችንም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለበቴ እንድትሆን ልክ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ አመቺ ሁኔታን በፈጠረልን ነበር። ለዚህም የሚያመች የትምህርት ስርዓት እንዲነደፍ ለማድረግ በበቃ ነበር። ይሁንና ግን ይህንን ከማድረግ ይልቅ አገራችንና ህዝባችን ተሽመድምደው እንዲቀሩ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው እንዲተገበር ያደረገው። በሌላ ወገን ግን የአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ፣ ቢሮክራሲውና ቴክኖክራቶች ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚያመች ፖሊሲ የትኛው መንገድ ነው ብለው ለመጠየቅ የሚችሉ ስላልነበሩ በቀላሉ ሊታለሉ ችለዋል። ስለሆነም ከአንዳንድ በተለይም የተወሰነውን የህብረተሰብ ጥቅም ክሚያስጠብቁ ለውጦች ባሻገር ገፍተው ለመሄድ አልቻሉም። ለዚህ ደግሞ የግዴታ የሚሊታሪውንና የፀጥታውን ኃይል በመገንባትና የአገዛዙን የመጨቆኛ መሳሪያ በማጠናከር በቀላሉ በአገዛዙ ላይ ተፅፅኖ ማሳደር ይችሉ ነበር። በነበራቸውም ተቀባይነት ለራሳቸው የሚሆኑ ስላዮችን በመመልመል በተለይም በአብዮቱ ወቅት ከፍተኛ ውዝግብ እንዲፈጠር ሁኔታውን አመቻችተዋል። የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካን በመጠቀምና የተወሰኑ ኃይሎችን በማስታጠቅ በአገራችን ምድር የርስ በርስ ጦርነት እንዲፈጠር ለማድረግ ችለዋል። ዕውቀት ባልተስፋፋበት አገር ውስጥ የአንድን አገር የመንግስት መኪናን በዚህ መልክ ማዋቀር ማለት ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይፈጠር ወይም እንዳይተገበር መሰናክል መፍጠር ነው። ስለሆነም ነው በእስራኤልና በአሜሪካን የሚሊታሪ ሳይንስ ብለው በሚጠሩት፣ በመሰረቱ ፖለቲካዊ አስተሳስብና ሳይንስን የማያስቀድመው ስልጠና በተግባር ላይ ሲመነዘር ያሉብንን በተለይም በብሄረሰብ ተሳበው የሚነሱ ችግሮችን ከማባባስ በስተቀር ስላምን የሚያስፈን ሁኔታ ሊፈጠር አልቻለም። ፖለቲካዊ አስተሳስብን ከማስቀደምና  ሳይንሳዊ ትንተና እየሰጡ የችግሮችን ምክንይት በመረዳት መፍትሄ ለመስጠት ሙከራ ከማድረግ ይልቅ ሁሉም ነገር በአመጽ ወይም በጦርነት ሊፈታ ይችላል ብሎ በማሰብ ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ ተገባ።  ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በሁሉም የፖለቲካ ተዋናይ ነን በሚሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች መንፈስ ውስጥ ሰርጎ የገባና እስካሁንም ድረስ ለመላቀቅ ያልቻለ አደገኛ አስተሳሰብ ለመሆን በቅቷል። አመጽ አመጽን ይወልዳል እንደሚባለው በእስራኤልና በአሜሪካን የሚሊታሪ አስተሳሰብ የሰለጠነው ኮማንዶ በተለይም በኤርትራ ውስጥ አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ከፍተኛ ዕልቂት በማካሄድ ነገሩ እንዲባባስና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የግዴታ ኤርትራ ከእናት አገሯ ለመገንጠል እንድትበቃ ተደርጋልች። ለዚህም ዋናው  ምክንያት ደግሞ በፖለቲካ ፍልስፍና ወይም ጥበብ አለመመራት ነው። በውጭ ኃይል መተማመን የሚያመጣውን አደጋ አለመረዳት ነው እዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ የከተተን። አሜሪካኖችም ይህን ዐይነቱን ፊዩዳላዊ የሆነ የአፄውን ፖለቲካ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከዚያም በኋላ ደርግ ስልጣን ላይ ሲወጣ  በዘመናዊነት  ፖለቲካና ፍልስፍና በመመራት የሰለጠነ ፖለቲካ ለማካሄድ እንደማይችል በሚገባ ያውቃሉ። ምክንያቱም በአገራችን ምድር ሰፋ ያለና የተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስላልተካሄደና የነቃ የህብረተሰብ ክፍልም ሊፈጠር ባለመቻሉ የመጨረሻ መጨረሻ እንደዚህ ዐይነቱ ውዝግብ መፈጠሩ የማይቀር መሆኑ ግልጽ ነበር። ስለሆነም ኮሙኒዝምንና አብዮቱን በማጥላላት ሁኔታውን ማባባስና ደርግንም  የባሰ አረመኔ እንዲሆን ማድረግ ዋናው ስልታቸው ነበር። በአጭሩ በዚህ ዐይነቱ የተንኮል ፖለቲካ ነው አንድን አገር ማዳከምና ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው። አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም በዓለም አቀፍ ደረጃ የህግ የበላይነት፣ የሊበራል አስተሳሰብ፣ የስቪል ማህበረሰብና የነፃ ገበያ እንዲስፋፋና እንዲተገበርም እንታገላለን ቢሉም ዋናው ዓላማቸው የበላይነታቸውን ማስፈን ብቻ ነው። በተቻለ መጠን በተለይም አንዳቸውም የጥቁር አፍሪካ አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ የሚገለጽ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚና ህብረተሰብ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። ስለሆነም በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የውክላና ጦርነት ማካሄድ ነው። አንድ አገርና አንድ ህዝብ በጦርነት ሲወጠሩ መንፈሳቸው በሙሉ በጦርነት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይደረጋል። ስላምን ስለሚያጡ ቁጭ ብለው የማሰብ ኃይላቸውን በመጠቀም ለመፍጠርና ስርዓት ያለው ማህበረሰብ ለመገንባት አይችሉምም። በመሆኑም ቀጫጫ ጭንቅላት ያላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች ስልጣን ላይ በማውጣትና በመደገፍ የአንድን ህዝብ ሰቆቃ ማባባስ ነው ዋናው የፖለቲካ ስልታቸው። ይህ ዐይነቱ ፖለቲካ በመሰረቱ የሬናሳንስን፣ የሬፍሮሜሽንና የኢላይተንሜንትን መሰረተ-ሃሳቦች የሚፃረር ነው።  ባጭሩ ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ የሚያደርጉና ምስኪን ህዝብ ርስ በርሱ እንዲጨራረስ የሚያደርጉ ኃይሎች ሰይጣናዊ መንፈስ ያላቸው ሰዎችና አገሮች ብቻ ናቸው።

ለማንኛውም ወደ ዛሬው ሁኔታ ስንመጣ እነአቢይ አህመድ የሚያካሂዱት የውንብድና ፖለቲካ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥርና እሳቤ ውጭ ነው ብሎ ማሰብ ከፍተኛ የዋህነት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው። መሳይ መኮንና ተጠያቄው ከፍተኛው ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት እንደሚሉት አሜሪካ ለአገራችንና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ ህወሃት በሁኔታው ተገዶ ስልጣን እንደዲለቅ ከተደረገ በኋላ ሙሉ በሙሉ መሳሪያውን በማስረከብና ትግራይን ከሚሊታሪ መሳሪያ ሙሉ በሙሉ በማላቀቅ ለማስተዳደር የሚያመች ሁኔታ በፈጠሩ ነበር። ጦርነትም ከፍቶ ከተሸነፈና ከተዳከመ በኋላ እንደገና ጦርነት ሲከፍትና የአማራውን ክልል ሲወር ከማስቆም ይልቅ በቀጥታ መሳሪያ ያቀብሉት እንደነበር ግልጽ ነው። የባይደን አስተዳደር ብቻ ሳይሆነ የአሜሪካ ግብረአበሮችና እንደ አውሮፓ አንድነት አንድ ላይ በመሆን ነው ከወያኔ ጎን በመሰለፍ በህዝባችን ላይ ጦርነት እንዲካሄድ ይገፋፉ የነበረው። በጊዜው እዚህ ጀርመን አገር፣ በርሊን ከተማ የሳይንስና የፖለቲካ ፋውንዴሽን ውስጥ ተቀጥራ ትሰራ የነበርች፣ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አንድነት ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች ተጠሪ የሆነች፣ በተለይም በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት እንዲስፋፋ የምታተገል ፕሮፈሰር ሬናተ ቬበር የምትባል ሴት ከወያኔ ጎን በመቆም ጦርነቱ ከተስፋፋ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ኢትዮጵያዊ ወደ ምዕራብ አውሮፓ ሊሰደድ ይችላል፤ ለዚህም መዘጋጀት አለብን እያለች ኃላፊነት የጎደለው ቅስቀሳ ታደርግ የነበረው እነዚህ ኃይሎች በሙሉ ዋናው ዓላማቸው ጦርነትን በቀጠናው በማስፋፋት የህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግና ከፍተኛ አለመረጋጋትን መፍጠር ነው። በአጭሩ የአሜሪካንና የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ዋና ዓላማ ሰላምና ብልጽግና በየአገሮች ውስጥ ማምጣት ሳይሆን አገሮችን በቀላሉ መቋጠሪያ በማያገኝ ጦረነት መያዝና ማሸት ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ብቻ ሳሆን እንደወንጀለኛም የሚያስቆጥር አስተሳሰብ ነው።

በአጭሩ በመሳይ መኮንንም ሆነ በተጠያቂው የከፍተኛ ዲፕሎማት የተሰጠው ዘገባና አስተያየት ሙሉ በሙሉ ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛና አዘናጊም ነው። በተለያዩ ጊዚያት ስልጣንን የያዙ የአሜሪካ አስተዳደሮችና ፕሬዚደንቶች አንዳችም ቦታ ላይ በእሴት በመመራት አልታገሉም። ለዓለምም ሰላም የቆሙበት ጊዜ የለም። ስለሆነም ቶፕ ዲፕሎማቱ የአሜሪካኖች እሴት ወይም ቫልዩ ሲልና፣ ለዚህም የሚቆሙ ናቸው ሲል ነገሩን አብራርቶ ለማስረዳት አልቻለም። ለስብአዊ መብት፣ ለሰላምና ለዕድገት የሚታገሉ ናቸው ማለቱ ነው? በግልጽ የተናገረው ነገር የለም። እንዲያው በደፈናው ብቻ ነው በመናገር ያደናገረን። በሌላው ወገን ከላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት፣ የአሜሪካን ዋናው የውጭ ፖለቲካ የበላይነትን ማስፈን ነው። በእኔ አስተሳሰብ ተገዛ ነው። እኔ ይህንን ብላ ስልህ መብላት አለብህ ነው። በዚህ ሰዓትም ተኛ ስልህ ነው የምተተኛው። በአጭሩ የአሜሪካ ቫልዩ ወይም እሴት በነፃ አታስብ ነው።  እኔ ብቻ ነኝ ይህችን ዓለም እንደፈለጉት የማሽከረክራት፤ ስለሆነም ዕውነተኛ ሰው እኔ ብቻ ነኝ፤ ሌላው በሙሉ ከሰው በታች የሆነ ነው የሚል ነው። የሚያሳዝነው ነገር መሳይ መኮንና ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተዋናይ ነኝ የሚለው ሁሉ ይህንን የአሜሪካንን እሴተ-አልባ ፖለቲካ አምነው መቀበላቸው ነው። ከአሜሪካኖች ውጭ የሚካሄድ ፖለቲካ የለም የሚል በአብዛኛዎቻችን መንፈስ ውስጥ ተቀርጿል። በተለይም ዕድሜያቸው ከስድሳ ዓመታት በላይ የሆኑና በአሁኑ ዘመን በአሜሪካ አገር ኗሪነታቸውን ያደረጉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቢሮክራቶችና ቴክኖክራቶች፣ እንዲሁም ለአሜሪካን የስለላ ድርጅት ሲሰሩ የነበሩና አሁንም ቢሆን አሜሪካንን የኢትዮጵያ አጋዥና የረጅም ጊዜ ጓደኛ የነበረች አገር አድረገው የሚያምኑና የሚቆጥሩ በዚህ ዐይነቱ የመሸነፍና የአገርን ብሄራዊ ነፃነት በማስደፈር አስተሳሰብ መንፈሳቸው የታነፀ ሁሉ የሚጋሩት አስተሳሰብ ነው። የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅምም የሚጠበቀው በዚህ ዐይነቱ ደካማ አስተሳስብ መንፈሳቸው በተቀረጸ ሰዎች ወይም ቡድኖች አማካይነት ነው። ስለሆነም የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም ሲባል ኢትዮጵያን ማጠንከር፣ ባህሏን ማደስ፣ ጠንካራ የህብረተሰብ ክፍል በመዋጣትና በማዳበር አገራችንን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ሳይሆን የውክልና ጦርነት በማካሄድ የሰውን ኃይልና በገንዘብም ሆነ በጥሬ-ሀብት የሚለካ ሀብትን በማውደም ህዝባችንን አቅመ-ቢስና ለማኝ ማድረግ ነ። ይህ ነው የአሜሪካን ኮር ቫልዩና የብሄራዊ ጥቅም መሰረተ-ሃሳብ። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                                                                                                                                                                  fekadubekele@gmx.de                                                                                        

                                                                                                                                                                                                                            www.fekadubekele.com