[gtranslate]

አገር ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ ወይስ በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ወደ

ገበያ ኢኮኖሚ የሚደረግ ጉዞ!

                                                                ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                የካቲት 17፣ 2020

 

Whether you can observe a thing or not depends on the theory which you use. It is the theory which decides what can be observed.” Albert Einstein

                              The ruling ideas are always and everywhere are the ideas of the ruling class. (Karl Marx)

 

መግቢያ

እ.አ.አ መስከርም 9፣ 2019 ዓ.ም ዶ/ር አቢይ በአፍሪካ ውስጥ አቻ የማይገኝለትና፣ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደምሳሌ ሊሆን የሚችል ብልጽግና እ.አ.አ እስከ 2030 ዓ.ም በኢትዮጵያ ምድር ዕውን እንደሚሆን አብስረዋል። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ አገር ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ(Homegrown Economy Reform) በመባል ሲታወቅ፣ በዐይነቱ „አገር በቀል ወይም ስር-ነቀል“ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም በመንግስት ከሚደገፍና የመንግስት ቁጥጥር ስር ከአለበት ኢኮኖሚ በመላቀቅ የግል-ባለሀብቶችን በማሳተፍ  ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ነው።

ይህንን አዲሱን አገር ቤት ውስጥ የሚበቅልና የሚያድግ ኢኮኖሚ ዕውን ለማድረግ እስካሁን ድረስ ኢኮኖሚው እንዳይንቀሳቀስ እንደማነቆ የያዙትን ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ዘዴዎችን ማስወገድና፣ አዲስና ዘመናዊ የአሰራር ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ የጥገና-ለውጡ ዐይነተኛ መሳሪያ ነው።    ይሁንና ግን በኢኮኖሚና በገንዘብ ሚኒስተር ዲኤታው በዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ዕምነትና አገላለጽ ባለፉት 15 ዓመታት በአብዛኛዎቹ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ትንታኔ መሰረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ተዓምር የታየበት ለመሆኑ ተናግረዋል።  በሌላ ወገን ደግሞ አዲሱ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ስልጣን ከመያዙ በፊት፣ በተለይም ከአንድ ዐመት በፊት አገሪቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትገኝ እንደነበር ሲያስረዱ፣ አዲሱ አገዛዝ ስልጣንን ከተረከበ ጀምሮ አገርበቀል ስራ በመሰራቱ ዛሬ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንገኛለን በማለት፣ በተለይም በሳቸውና በመንግስታቸው አገላለጽ ይህንን አገር ቤት ውስጥ የሚበቅልና የሚያድግኢኮኖሚያዊ የጥገና ለውጥ ተግባራዊ ለማድረግ አገዛዙ መነሳሳቱና፣ በተለይም የውጭ ኃይሎች እንዲተባበሩ ጥሪውን አቅርበዋል። በተለይም የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን በሚባለው አዳራሽ ውስጥ ለውጭ ዲፕሎማቶችና ኮሚሽኑ ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩ የውጭ አገር ሰዎችና ኢትዮጵያኖች በሰጡት በፓወር ፖይንት በተደገፈ ገለጻ የአዲሱን የኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ አስፈላጊነት በማስመር፣ አገሪቱ ያላትን የልማት ዕምቅ ለማበልጸግ እንደሆነ ለአዳማጮቹ ተናግረዋል።  በዚህ መሰረት አገር ቤት ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት በሶስት መሰረተ-ሃቦች ላይ አትኩሮ እንደሚያደርግና፣ በእነዚህ ዙሪያ አገር-በቀል የጥገና ለውጥ እንደሚያካሂድ ለአዳማጮቹም ሆነ ለሌላው ኢትዮጵያዊ በሌላ ወቅት አብስረዋል። እነዚህም፣ 1ኛ) የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ማድረግ፣ በተለይም የፋይናንስ መስኩን ማሻሻል፣ 2ኛ) የመዋቅር ለውጥ ማድረግ (Structural Reforms) ፣ 3ኛ) የኢኮኖሚ መስኮችን፣ ማለትም የማኑፋክቸሩን፣ የእርሻውንና የአገልግሎት መስኩን ማሻሻል የሚሉ ናቸው። በአጠቃላይ ሚኒስተሩም ሆነ በሚኒስተር ዲኤታው ዕምነት መሰረት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መሰረተ-ሃሳቦች ተግባራዊ ከተደረጉና፣ በተለይም ደግሞ ኢኮኖሚው በደንብ እንዳያድግ እንደማነቆ የያዙት ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ዘዴዎች ከተወገዱ እ.አ.አ በ2030 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሌላ ተዓምር የሚታይባትና፣ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደምሳሌ ልትታይ እንደምትችል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

ከዚህ ስንነሳ ይህ አዲሱ የጥገና ለውጥ 1ኛ) የቱን ያህል ቀደም ብሎ በአገራችን ምድር የህውሃት አገዛዝ ስልጣን ከያዘ ጀምሮና፣ በዶ/ር አቢይ አገዛዝ እስኪተካ ድረስ በይዘትም ሆነ በቅርጽ እንደሚለይ ወይም ተመሳሳይነት እንዳለው እንመርምር። 2ኛ) አዲሱ የጥገና ለውጥ የቱን ያህል አገር ቤት ውስጥ የሚያድግ መሆኑና፣ አገር ቤት ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጠጋ ብለን እንመልከት። 3ኛ) ስለሆነም አዲሶቹ መሪዎቻችን እንደሚሉት በእርግጥስ በአገራችን ምድር እስከ 2030 ዓ.ም የገበያ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ወይ? ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ በፖሊሲ አውጭዎች ዕይታ የገበያ ኢኮኖሚ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት እሞክራለሁ። 4ኛ) በዕርግጥስ በዚህ ዐይነቱ የጥገና ለውጥና በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት በመላቀቅ ወደ ብልጽግና ሊያመራ ይችላል ወይ? አገራችንስ እንደ ማህበረሰብና እንደ ህብረተሰብ በፀና መሰረት ላይ ለመገንባት ትችላለች ወይ? በዚህ ዐይነት የጥገና ለውጥ አማካይነትስ ተከታታይነት ያለው(Sustainable Development) የኢኮኖሚ ዕድገትና ህብረተሰብ መገንባት ይችላል ወይ? 5ኛ) በጸሀፊው ዕይታ ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በምን መሰረተ-ሃሳቦች ላይ መደገፍ ይኖርበታል፤ በአጠቃላይ ሲታይ ምንስ መምሰል አለበት? የሚሉትን ጠጋ ብለን እንመርምር።

ትላንትም ዛሬም ወደ ገበያ ኢኮኖሚ የሚደረግ ጉዞ!

በአገራችን ምድር ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በአፍሪካ ምድርም ስማቸው እየተለዋወጠ በይዘት ግን ተመሳሳይነት ያላቸውና፣ ዓላማቸውም የገበያን ኢኮኖሚ ዕውን ለማድረግ በሚል ስም በየአስር ዓመቱ አዳዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ይወጣሉ፤ ተግባራዊም ይሆናሉ። እነዚህ ፖሊሲዎች ከመርቀቃቸው ጀምሮ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው እስኪቀበለዉና አረንጓዴ መብራት እስኪያሳይ ድረስ ስንትና ስንት ሀብት የሚፈስበት ብቻ ሳይሆን፣ በጥገና ለውጦቹም አማካይነት ወደ ውጭ ሀብት በመፍሰስ አህጉሪቱም ሆነ አገራችን ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ያልታየባቸውን፣ የህዝቡም ኑሮ ያልተሻሻለበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህም የሆነበትና የሚሆንበት ዋናው ምክንያት የፖሊሲው አውጭዎችና ወሳኞች የየአገሩ መንግስታትና ምሁራኖች ሳይሆኑ የወጭ ኃይሎች፣በተለይም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ በአጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው በመባል የሚታወቁት በመሆናቸው ነው። እነዚህ ኃይሎች ደግሞ የሚመሩበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይንሳዊ ያልሆነና ፍልስፍና አልባ በመሆኑ፣ ወደድንም ጠላንም በየአገሮቹ ውስጥ አፍጦ አግጦ ለሚታየው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር መፍትሄ ከመሆን ይልቅ ችግሩን የባሰውኑ ያባብሰዋል።  በየጊዜው የሚወጡትና መንግስታት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በቅርጽ ለየት ያሉ ቢመስሉም በይዘታቸው ግን አንድ ዐይነት የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ናቸው። ለማንኛውም በየጊዜው ፖሊሲዎች ሲወጡና ተግባራዊ ሲሆኑ ይኸው አድገን፣ ጺም አውጥተን፣ ሸብተንና ጡረታ ለመውጣት ተቃርበን እስቲ ሞታችንን አሳምርልን እያልን በመጸለይ ላይ እንገኛለን። እኛ እየተለወጥን ስንሄድና ስናረጅ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የተቀሩት የአፍሪካ አገሮችም ሆነ የአገራችን ኢኮኖሚ መሰረታዊ ለውጥ ሳያይና ህዝቦቻቸንም በድህነት ሲማቅቁና፣ የሚችሉት ደግሞ ወደ ውጭ አገር ሲሰደዱና ዕድል ያጋጠመው አሜሪካም ሆነ አውሮፓ በመምጣት ደፋ ቀና ሲል እንመለከታለን። ይህ ዐይነቱ ተደጋጋሚ የላቦራቶሪ ዐይነት ሙከራና ህዝቦች ደግሞ በድህነትና በስደት ዓለም ውስጥ የሚማቅቁት የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብትና ለእርሻ መሬት የሚሆን ለም መሬት ባለበትና፣ ከአንዳንድ አገሮች በስተቀር ዝናብም ሆነ ወንዞች እንደልብ በሚገኙበት አህጉር ነው። ከሁለት ወር በፊት ልጃችን ለስራ ጉዳይ ወደ ሌጎስ፣ ናይጄሪያና ወደ አክራ፣ ጋና ታመራለች። ሁለቱ ከተማዎች ሁለት ሳምንታት ያህል በቆየችባቸው ጊዜያት የታዘበቸው ነገር የደሃው ቁጥር መብዛትና የትራፊክ መጨናነቅና የመኪና ብዛትን ነው። እንግዲህ ሁለቱም አገሮች በጥሬ-ሀብት የተትረፈረፉና፣ በተለይም ደግሞ ናይጀሪያ ከአህጉሩ በዘይት ምርትና ሽያጭ ከፍተኛውን ቦታ የያዘች አገር ነች። ይሁንና ናይጀሪያም ሆነ አሁን በቅርቡ ከወርቅ መምረት ባሻገር የዘይት ክምችት የተገኘባትና የሚወጣባት ጋና ለህዝቦቻቸው አስተማማኝ የሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሰረት በፍጹም ሊጥሉ አልቻሉም። በሁለቱም አገሮች ሆነ በአገራችን ምድር ጥቂቶች የተንደላቀቀ ኑሮ ሲኖሩ፣ ህዝቦቻቸው ደግሞ እንደሁለተኛ ዜጋ በመታየት ተንቀውና ተዋርደው እንዲኖሩ ተገደዋል። ናይጄሪያም ሆነ ጋና ከቅኝ-አገዛዝ ከተላቀቁ 60 ዐመት ያህል ቢጠጋቸውም፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር ያሉ በመምሰል ሀብታቸው የሚዘረፍበትን ሁኔታ እናያለን። የአገራችንም ሁኔታ ከእነሱ የሚለይ አይደለም። በተለይም በዕርዳታ ሰጪዎች ቁጥጥር ስር የወደቀች አገር ነች ማለት ይቻላል።

በተለይም የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ነገር ከጥቂት ዐመታት በስተቀር አንድም ጊዜ በቅኝ አገዛዝ ስር አልወደቀችም ብለን የምንዝናናባትና የምንኮራባት አገራችን የራሷን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማውጣት ተስኗትና በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ወድቃ መሳቂያና መሳለቂያ መሆኗን ስናይ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም ባለፉት 28 ዓመታት ጎልቶ የወጣና፣ ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ የአገራችን ዕድል የሚወሰነው በአገዛዙ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች እንደሆነና ቁጥጥርም እንደሚደረግበት እንመለከታለን።

ከዚህ ስንነሳ ወደ ዛሬው ኢኮኖሚያዊ የጥገና ለውጥ ማሻሻያ ስንመጣ መሰረታዊ ለውጥ ለመምጣት እንደማይችል ከአሁኑ መናገር እንችላለን። የህዝባችንም ኑሮ ዛሬ ካለበት ሁኔታ ፈቀቅ እንደማይል ከፖሊሲው ይዘትና ፖሊሲውን ካወጡትና ከበላይ ጠባቂዎቻቸው ባህርይ መረዳት እንችላለን። ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት አለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ በቅርጽም ሆነ በይዘት ከድሮው የተለየና አዲስ ሃሳብን የያዘ ነው ተብሎ የቀረበልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ ህወሃት 27 ዓመት ያህል ተግባራዊ ካደረገው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንም ዐይነት አይለይም። የፖሊሲው አውጭዎችም ሆነ የበላይ ጠባቂዎቻቸው የሚዘነጉት ነገር ይህንን ጉዳይ ነው፤ አሊያም ደግሞ አይገባቸውም ብለው እያታለሉን ነው። ከ28 ዓመት በፊት ህወሃት ስልጣን ሲይዝ የተነገረው ዕድገት ለማምጣትና ሰፊውን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት ያለው አማራጭ መንገድ የገበያ ኢኮኖሚ ብቻ ነው የሚል ነበር። ይሁንና ግን ከ27 ዐመት የነፃ የገበያ ሙከራ በኋላና በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ስም ሚዛናዊነት ያለውና የተስተካከለ፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያ የተገነባ ሳይሆን፣ የተዘበራረቀና ብዙ ሀብት የወደመበትና፣ ጥቂቶች በሀብት ናጠው፣ በአንፃሩ ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ወደ ድህነት ዓለም የተገፈተረበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በ27 ዓመት የገበያ ኢኮኖሚ ሙከራ ዘመን ህዝባችን መጥፎ ከሚባሉ ፣ ለሰው ጭንቅላት የሚዘገንኑና ባህልን አውዳሚ ከሆኑ ነገሮች ጋር ሁሉ እንደተለማመደና በራሱ ላይ እንዳይተማመንና ብሄራዊ ነፃነቱ እንዲገፈፍ ያደረጉ ነገሮችን አይቷል። ከመሬቱ ተፈናቅሏል፤ ለልማት እየተባለ በአዲስ መጤዎች ቤቱ እየፈራረሰ ሜዳ ላይ እንዲጣል ተደርጓል። ከዛሬ 28 ዐመት በፊት በገበያ ኢኮኖሚ ስም የወጣው ፖሊሲ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ የተደገፈና ቡራኬ ያገኘ ሲሆን፣ ይህንንም የዓለም ኮሙኒቲው የሚባለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሱን ውስጣዊ መንግስት በማቋቋም በተለይም እንደኛ የመሳሰሉ አገሮችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠረው ያፀደቀው ነው። በተለይም ትችታዊ አመለካከት (Critical thinking) ያለውና በዓለም አቀፍ ፖለቲካ (International Poltical Relationship) የሰለጠነና የሶስይሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው የሚገነዘበው ነገር አንድ አገዛዝ የፈለገውን ያህል ቢመጻደቅምና እኔ ነኝ መሪያችሁ ብሎ ቢዝናናም እንደኛ አገርና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያሉት አገዛዞች በሙሉ ራሳቸውን የቻሉና ራሳቸውም አውጥተውና አውርደው፣ እንዲሁም ተከራክረው እንደዚህ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው አገራችንን ሊያሳድጋትና ህዝባችንን ከድህነት አላቆ ብሄራዊ ነፃነቱ የተከበረ አገር መገንባት የሚያስቸለው ብለው ወደ ተግባር ሲሻገሩና ህዝቡን ሲያስለፉ አይታይም። ፖሊሲው ከወጣ በኋላም ለህዝብም ሆነ ለምሁራን ይፋ ከመደረጉ በፊት ለአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቀረበው በመጀመሪያ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ይወቀው ከሚለው ስሌት የተነሳ ነው።

ያም ሆነ ይህ ይህንን ፖሊሲ ያወጡት የኢኮኖሚና የፊናንስ ሚኒሰትሩ ሰራቶች ወይም ሚኒስተር ዲኤታው፣ እንዲሁም ደግሞ ለኧርንስት ኤንድ ያንግ (Ernst and Young) ተቀጥሮ የሚሰራውና ሚኒስተሩን የሚያማክረው የአሜሪካ ዜግነት ያለው ኢትዮጵያዊ፣ እንደዚህ ዐይነቱን ፖሊሲ ከማውጣታቸው በፊት፣ 1ኛ) የዛሬ 27 ዓመት ምን ዐይነት ፖሊሲ እንደወጣ በደንብ መመርመር ነበረባቸው። 2ኛ) የፖሊሲውን ዐይነት ካወቁ ደግሞ ፖሊሲው የተፈለገውን ውጤት አላመጣም ከተባለ የፖሊሲውን ጉድለት ብቻ ሳይሆን፣ ከአገራችን የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ፣ የኢኮኖሚ አወቃቀርና የህብረተሰብ ዕድገት እንዲሁም የባህል ሁኔታ አንፃር በመመርመር አዲስና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ሁለ-ገብ ፖሊሲ ማውጣት አለባቸው። 3ኛ) የአዲስ አበባን ሁኔታ ወይም አንዳንድ ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በቡድን በቡድን በመሆን ቢያንስ ሶስት ወር ያህል በአገሪቱ ምድር በመዘዋወርና ህዝባችን እንዴት እንደሚኖርና፣ ከተማዎችና መንደሮች እንዴት እንደተገነቡ ከመረመሩ በኋላ ኋላ-ቀርነትና ድህነት የሚንፀባረቅባቸው ከሆነ ሁኔታው ለምን እንደዚህ ሆነ በማለትና በመመርመር ከዚህ ዐይነቱ ኋላ-ቀርነትና ድህነት የሚያወጣ አዲስና ፍቱን ፖሊሲ ማውጣት የግዴታ ነው። ይህንን ሳያደርጉ በተወሰነ የስታትስቲክስ አሃዞች ላይ ተመስርቶ የሚወጣ ፖሊሲ እንደፖሊሲ ሊቆጠር አይችልም። ማቲማቲካል ሞዴሎችና ስታትስቲክስ የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀር ወይም የሚገኝበትን አጠቃላይ ሁኔታ መግለጽ ስለማይችሉ በዚህ መልክ የሚወጣ ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከሽፎ ይቀራል።

ይህ ብቻ አይደለም፣ የፖሊሲው አውጪዎችም ሆነ እምባ ጠባቂዎቻቸው የአገራችን የኢኮኖሚ አወቃቀር ምን እንደሆነ ሊነግሩን በፍጹም አልቻሉም። ማንኛውም ህብረተሰብ እንደማህበረሰብ ሲኖር የሚያንቀሳቅሰው አንድ ዐይነት የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ወይም ደግሞ የተሰበጣጠሩና ህዝቡ ራሱን የሚጠግንበት (Reproduction Base) እዚህና እዚያ የሚገኙ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ወደ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ ስንመጣ አነሰም በዛም አንድ ወጥ የሆነ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የካፒታሊስት ስልተ-ምርት አለ። ይህ ዐይነቱ ስልተምርት በዐይነትም ሆነ በውስጠ-ኃይል ጥልቀቱ ከእኛው ወደ ኋላ ከቀረና ተሰበጣጥሮ ከሚገኝ ኢኮኖሚ በብዙ እጅ ይለያል። በአብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ አብዛኛው ህዝብ ተቀጥሮ የሚሰራና ተከታታይ ገቢ ያለው ሲሆን፣ በአገራችን ደግሞ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከእጅ ወደ አፍ (Subsistence Economy) በሚደገፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚኖር ነው። በተጨማሪም የካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚ ብሄራዊ ባህርይ ያለውና እርስ በእርሱ የተሳሳረ ሲሆን (Value-added chain) ፣ የአገራችን ኢኮኖሚ የተሰበጣጠረና የሚደጋገፍ አይደለም። አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ለውስጥ ገበያ ወይም ለብሄራዊ ኢኮኖሚ የሚያመች በደንብ የተገነቡ ከተማዎችና፣ ከተማዎችንም ሆነ የተለያዩ ክፍለ-ሀገራትን የሚያያዙ የተለያዩ የመመላለሻና የመገናኛ መስመሮች፣ ባቡርና ሌሎችም ሰውንና ዕቃን የሚያጓጉዙ ባቡሮችና የአገር ውስጥ መርከቦች ሲኖራቸው፣ የእኛው አገር ግን አሁንም ቢሆን ለገበያ ወይም ለካፒታሊስት ኢኮኖሚ የማያማቹ የማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ዐይነት የሚመስሉ መንደሮችና ቅጥ-የሌላቸው ከተማዎች ነው ያሉት። በዚህም ምክንያት የተነሳ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ኢኮኖሚ የሌላት አገር ናት። ኢኮኖሚውም ማክሮ የሚባል ባህርይ የለውም። ይህ ሁኔታ ደግሞ የዓለም ኢኮኖሚ ግፊት ሲጨመርበት እዚያ በዚያው የሚንደፋደፍና ተቀጥያ የሚሆን እንጂ፣ የሰፊው ህዝብ የኢኮኖሚ መሰረት በመሆን ወደ ብሄራዊ ባህርይ የመሸጋገር ዕድል በፍጹም አያገኝም። ስለሆነም ሁለቱም፣ የካፒታሊስት አገሮችና የአገራችን ኢኮኖሚ በተለያየ የኢኮኖሚ ህግና ሎጂክ የሚተዳደሩ ናቸው ማለት ነው። ሁለቱም በዐይነትም ሆነ በውሰጠ-ኃይል (Dynamism) ስለሚለያዩ የቀውሱም ዐይነትና ምክንያት ይለያያል።

ለምሳሌ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች የሚከሰተው ቀውስ ኮንጀክቸራል ወይም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መቀዝቀዝና የመዋቅር ቀውስ ነው። ኮንጀክቸራል ቀውስ ማለት ደግሞ የኢኮኖሚው ዕድገት ከፍና ዝቅ በሚል የሚገለጽ ሲሆን፣ በተለይም ሰራተኛው ከስራ-መስኩ የሚባረርበት ሁኔታና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የተመረቱ ዕቃዎች እንደድሮው የማይሸጡ ከሆነ አብዛኛዎቹ አምራች ከበርቴዎች የምርታቸውን ክንውን ይቀንሳሉ፤ ማለትም በዝቅተኛ ካፓሲቲ እንዲያመርቱ ይገደዳሉ። ይህ ዐይነቱ ቀውስ ከብዙ ነገሮች ጋር የተያዘ በመሆኑ፣ ብድር ሰጪ ባንኮችና ነጋዴዎችም ሆነ የጥሬ-ሀብት አቅራቢዎች ይጎዳሉ። በዚህ መልክ አጠቃላዩ ኢኮኖሚ ይጎዳል ማለት ነው።  የመዋቅር ቀውስ የሚባለው ደግሞ በተለይም እንደ ዲንጋይ ከሰልና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መቀነስ ሲሆን፣ በተለይም እነዚህ መስኮች ከውጭ በሚመጡ የዲንጋይ ከሰሎችና የብረታ ብረት ውጤቶች በውድድር ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ስለሚዳከም አንዳንዶቹ ይዘጋሉ። ስለሆነም በተለይም በተወሰኑ አካባቢዎች የተተከሉና የሚንቀሳቀሱ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች በእንቅስቃሴው ድክመት ከስራ ቦታቸው የመባረር ዕድል ያጋጥማቸዋል።  በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከአየር መዛባት ጋር የተነሳ በተለይም እንደ ፀሀይ፣ ነፋስና ውሃ የመሳሰሉት አማራጭ የኃይል ማመንጫዎች ቦታውን በመያዝ ብዙዎች የዲንጋይ ከስል ማውጫዎችና ፋብሪካዎች እየተዘጉ ነው። ስለሆነም በድሮዎች ትራዲሽናል በሆኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ፈንታ አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እየተተኩ ነው። አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ገና በማገገም ላይ ናቸው።

በዚህ መልክ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ከዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መዳከምና ከመዋቅር ቀውስ ለመላቀቅ ባለፉት 50 ዐመታት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃዎችን በማለፍ ዛሬ ከፍተኛ የሆነ ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አብዛኛዎች ኢንዱስትሪዎች በኮምፒዩተር እየተደገፉ የሚያመርቱ ናቸው። ብዙ የኢኮኖሚ ንዑስ መስኮች በመያያዝ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ተለውጧል። በኃይል አስለላፍ ምክንያት የተነሳም እንደዚሁ የካፒታሊስት መንግስታት ሚና እየተለወጠ መጥቷል። ከ1945- 1970 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች የመንግስታት ሚና ጎልቶ የሚታይ ነበር። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ መንግስታት ጣልቃ-ገብ ፖሊሲ (Interventionist Policy) በመከተል ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተል ሚናቸው አጠቃላይ ሀብት እንዲዳብር ከማድረግ ይልቅ በቀረጥና በተለያዩ ፖሊሲዎች አማካይነት ሀብት ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ከፍተኛው እንዲሸጋሽግ ሁኔታውን አመቻችተዋል። ይሁንና አሁንም ቢሆን የመንግስታት ሚና ሙሉ በሙሉ የተዳከመ አይደለም። በተለይም እንደ 2008 ዓ.ም የመሰለ የፋይናንስ ቀውስ ሲከስት ቀውሱ እንዳይባባስ በማለት ባንኮችንና ኢንዱስትሪዎችን የሚያድን ፖሊሲ እንዲወስዱ ይገደዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምርምሮች በመንግስት የሚደገፉና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተባብረው የሚሰሩ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በአውቶኖመስ ደረጃ ቢሰራምና የራሱ የሆነ የውስጥ አሰራር ህግ ቢኖረውም መንግስታት በተለያየ የፖሊሲ መሳሪያዎች በመደገፍ በተዘዋዋሪ ጣልቃ ይገባሉ።

ስለሆነም የአገራችንም ሆነ የካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚዎች ቀውስ ወይም ህመም ሲያጋጥማቸው መፈወሻቸውም ሆነ የሚሰጣቸው መድሃኒትና በሽታውን የመመርመሪያ ዘዴ ይለያያሉ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነውን የሞኔተሪ ፖሊሲ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ አገርና ኢኮኖሚ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ በፍጹም አይቻልም። በሌላ አነጋገር፣ ነቀርሳ ለያዘው ሰው የጉንፋን በሽታ ለያዘው ሰው የሚሰጠውን መድሃኒት በፍጹም አይታዘዝለትም። የመመርመሪያው ዘዴም እንደዚሁ ይለያል።  ይህ የሚሆን ከሆነ በሽተኛው በሽታው ይጠናበትና ለሞት ይዳረጋል። ስለአገሮችም ስናወራ በተለያየ የህብብረተሰብ ህግ የሚተዳደሩና፣ የተለያየ የኢኮኖሚ ስርዓት ያላቸው ሁለት አገሮች ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አደርጋለሁ ቢሉ አንዱ አገር ሊሰራ የሚችለው ሌላ አገር ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ያልተፈለገ ውጤት ነው የሚያመጣው።  በሌላ ወገን ግን፣ በየትኛውም አገር ተግባራዊ የሚደረግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የኃይል ሚዛን ውጤትና ርዕዮተ-ዓለማዊ ባህርይ አለው። በኢኮኖሚ ፖሊሲ ታሪክ ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ የሚጠቅም ፖሊሲ ተግባራዊ የሆነበት ጊዜ የለም። በተለይም እ.አ.አ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ንጹህ በንጹህ የርዕዮተ-ዓለም ባህርይ መውሰድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በራሱ በካፒታሊስት አገሮች ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ከፍተኛው የህብረተሰብ ክፍል የሀብት ሽግሽግ እንደተደረገና፣ በከፍተኛ ደረጃ በሀብታምና መጠነኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል ያለው የገቢ ልዩነት እየጎላ እንደመጣ እንመለከታለን። ለምሳሌ አሜሪካን አገር 1% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል 90% የሚሆነውን ገንዘብና ሌላ የማይንቀሳቀሱ ሀብቶችን ሲቆጣጠር፣ በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ደግሞ ከ5-10% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል 80% የሚሆነውን በገንዘብ የሚተመንና ተጨባጭ ሀብቶችን ይቆጣጠራል። ይህም ማለት በአብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ሰፊው ህዝብ ሀብት የማፍራት ዕድል በፍጹም የለውም። በስም ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ነው ቢባልም የገበያው ኢኮኖሚ እዚያው በዚያው 80% የሚሆነውን ህዝብ ከሀብት አፍሪነት የሚያገልና ዘለዓለማዊ ጥገኛ የሚያደርገው ነው። ምክንያቱም የገበያ ኢኮኖሚ በአንድ በኩል በውስጡ ሀብት በጥቂት ሰዎች እጅ እንዲከማች የሚያደረግ ውስጣዊ-ኃይል ወይም መሳሪያ (built-in mechanism) ያለው ሲሆን፣ በሌላው ወገን ደግሞ መንግስታት በሚያወጡትና ተግባራዊ በሚያደርጉት የሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት አብዛኛውን ጊዜ ሀብት ከደሀው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ሀብታሙ እንዲንሸራሸር ያደርጋል። በዚህ መልክ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ግልጽ የሆነ የሀብት ልዩነት ሲኖር፣ በተለይም ጡረታ የወጡ ሽማግሌዎች በተሰወረ ድህነት ይሰቃያሉ። ከዚህ በላይ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በወለድና በትርፍ አማካይነት የበለጠ ገንዘብ ወይም ሀብት ታገኛለህ እያሉ ከህዝቡ በሚሰበስቡት ገንዘብ በተለይም መሬትንና ቤቶችን ሲቆጣጠሩ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በህዝቡ ላይ ጭነት ያደርጋሉ። ባጭሩ ኢኮኖሚው ነፃና ማንም ሰው በእኩል ደረጃ ሊወዳደር ይችላል ተብሎ ቢሰበክም፣ ባንኮች፣ የሀብታሞችን ሀብት የሚያስተዳድሩ ሄጅ ፈንድስ የሚባሉ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ናቸው አብዛኛውን የኢኮኖሚ መስኮች የሚቆጣጠሩት።

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ ቀድሞም ሆነ በዛሬው ወቅት ፖሊሲ አውጭዎችና የዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ ባጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው የሚባሉት ዓላማ አድርገው የሚነሱት እያንዳንዱ አገር የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ አለበት የሚል ነው። በእነሱ ሎጂክና ተጨባጭ ሁኔታዎችን አነባበብ እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ የተጓዘበት ታሪክ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ ቅንጅት፣ ባህልና የህሊና አወቃቀር የለውም። በእነሱ አመላከከትና አስተሳሰብ የሰው ልጅ በሙሉ ተመሳሳይ በሽታ ስላለው የሚታዘዝለትም መድሃኒት አንድ ዐይነት መሆን አለበት ከሚለው ሎጂክ ስለሚነሱ፣ በየአንዳንዱ አገር የሚኖር ህዝብ የመጨረሻ መጨረሻ አንድ ዐይነት የፍጅታ አጠቃቀምና ባህርይ አለው። ፍላጎቱም ሆነ ምኞቱ፣ ፍላጎቱን ማሳደግ (Utility maximization) ስለሆነ በሁሉም አገር የሚኖር ህዝብ አስተሳሰቡ የሚደነገገው በዚህ ዐይነቱ የነፃ ገበያ ህግ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ ካፒታሊስት በመዋዕለ-ነዋይ ክንውን ውስጥ የሚሳተፈው ከፍተኛውን ትርፍ (Profit Maximaization) ለማግኘት ነው።  ይህም ህግ ተፈጥሮአዊ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ጥቅሙን ከማሳደድና ከመስገብገብ ውጭ ሌሎች መንፈሳዊ ፍላጎቶች (Spiritual Needs) የሉትም። ስለሆነም ሁሉም አገር የገበያን ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ከዚህም በተጨማሪም በግልጽ የሚታየውን በካፒታሊስት አገሮች ያለውን ልዩነትና፣ የካፒታሊስት አገሮችን ኢኮኖሚ ውስጣዊ ህግና በእንደኛ አገር ያለውን ኢኮኖሚ ልዩነት ለመረዳት በፍጹም አይችሉም፤ ወይም አይፈልጉም። በዓለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ በዓለም ባንክና በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚ በሰለጠኑ ሰዎች ዕምነት የገበያ ኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ ከታሪክ፣ ከባህል፣ ከልምድ፣ ከስነ-ልቦና፣ ከአደረጃጀትና በምድር ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ተነጥሎ የሚታይናና፣ በጊዜና በቦታ የማይለካ ነው። ትላንት የነበረ፣ ዛሬ ያለና ለዘለዓለምም የሚኖር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ፣ ለምሳሌ ለኢኮኖሚ ዕድገት መሰናክል የሚሆነውን የመንግስት መኪናና፣ ይህ ዐይነቱ የመንግስት መኪና ከውጭው ዓለም ጋር በመተሳሰር በድሀ አገሮች ውስጥ የተስተካከለና ውስጣዊ-ኃይል ያለው ኢኮኖሚ እንዳያድግ እንቅፋት ስለመሆኑ በፍጹም አያነሱም። ስለሆነም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ በኢኮኖሚ ስሌት ውስጥ የማይገባና የማይነካም (God given) ነው። በአንድ አገር ውስጥ በገበያ ኢኮኖሚ የሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲታይ ከተፈለገ መንግስት ከኢኮኖሚ ውስጥ ራሱን ማግለል አለበት። የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ለዕድገትና ለገበያ ኃይሎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ እንቅፋት ነው። ይህ ዐይነቱ አደገኛ አስተሳሰብና፣ የየአገሮችን የኢኮኖሚ አወቃቀርና የህዝብን የመጠገኛ መሰረት (Reproduction Base) ሳይመረምሩና ሳያጠኑ እያንዳንዱን አገር እያስገደዱ ይህንን ካላደረጋቸሁ ብድር ወይም ዕርዳታ አንሰጣችሁም፤ ካለበለዚያ ደግሞ ጦርነት እንከፍትባችኋለን እያሉ በማስፈራራት ብዙ አገሮችን እያተራመሱና ለራሳቸው ለካፒታሊስት አገሮችም አደገኛና አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረባቸው ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በግልጽ የሚታየው የቀኝ ኃይሎች መንሰራራትና መበርታት፣ እንዲሁም ከሌላ አገር የመጡ ሰዎችን መጥላት ከዚህ ዐይነቱ ገደብ የሌለው ጣልቃ-ገብነትና በሁሉም አገሮች ውስጥ የነፃ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት፣ ሁሉም አገሮች በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው ከሚለው ግፊት የመነጨ ነው። በሌላ አነጋገር፥ ሁሉም አገሮች ታሪክና ባህል የሚሰራባቸው፣ ህዝቦችም ግብረ-ገብነትና ስነ-ምግባር ያላቸው ሳይሆኑ አገሮች ወደ ኒዎ-ሊበራል ገበያነት(Neo-Liberal Supermarket) በመለወጥ ከቁጥጥር ውጭ መውጣት አለባቸው። በሌላ አነጋገር፣ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮችና ሃይ-ቴክ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር የወደቁት የካፒታሊስት መንግስታት በአንድ በኩል የህግ የበላይነት እያሉ እየሰበኩ፣ በሌላው ወገን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ አናርኪዝም እንዲስፋፋ ግፊት ያደርጋሉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የየአገሮችን የማምረት ኃይልና ህዝቦቻቸውን የመመገብ ብቃትነት ሲያዳክመው፣ በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት (Sustainable Economic Development) ያስፈልጋል ብሎ ያወጣውን 17 ነጥቦች እንዳለ የሚፃረር ነው።

አሁንም ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ በየጊዜው ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉት ኃይሎች ትዕዛዝ ከመቀበልና ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርገው ሁኔታዎችን ከማዘበራረቅ በስተቀር አንድም ቦታ ላይ ቆም ብለው ጥያቄ በማንሳት የራሳቸውንና የዓለም ኮሙኒቲውን ድርጊት ለመመርመር በፍጹም አይቃጡም። ለምንድነው ድህነት የተስፋፋው? በምንስ ምክንያት ነው በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ህዝብ በትላልቅ ሆቴል ቤቶች በራፍ ላይ በመቀመጥ የሚለምነው? ብለው ጥያቄ ለመጠየቅና መልስም ለማግኘት በፍጹም አይጥሩም። ስለሆነም አሸብርቆ በፓወር ፖይንት የቀረበውን ዲያግራም ስንመለከት በፖሊሲው አወጣጥ ውስጥ ለየት ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ኢኮኖሚስቶች፣ ሶስዮሎጂስቶች፣ ፈላስፋዎችና የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች እንዳልተካተቱበት በቀላሉ መረዳት እንችላለን። በተለይም ደግሞ የሶሶዮሎጂ ጥናትና ምርምር ባልተለመደበት እንደኛ ባለው አገር ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሰዎች ፍላጎት ወይም የሰውን ፍላጎት ከማሟላት ውጭ ስለሚታይ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ዛሬ በአገራችን ምድር የምናየውን የሰው ከሰው ግኑኝነት፣ ድህነትና የማያስፈልጉ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔዎች፣ ሀብት ማባከንና ከተማዎችንም ሆነ በአጠቃላይ ሲታይ አገርን ማዘበራረቅና ህዝቡ ወዴት እንደሚጓዝ እንዳያውቅ የማድረግ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ መንግስትና ፖሊሲ አውጭዎች እራሳቸው የፈጠሩትን ሁኔታ በሌላው ላይ በማሳበብ በህዝቡ ላይ ጦርነት ያውጃሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝባችን በግልጽ ከሚታይ በሚሊታሪ የተደገፈ ጦርነት ብቻ ሳይሆን፣ የስነ-ልቦና፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የባህል ጦርነት ታውጆበት እንደ ማህበረሰብና እንደ ህብረተሰብ እንዳይኖር ለመገደድ በቅቷል። ከዚህ አልፈን የፖሊሲውን ይዘት በካፒታሊስት የገበያ ኢኮኖሚ መነፅር በምንመረምርበት ጊዜ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚከናወንና እርስ በእርሱ በሚያያዝ የኢኮኖሚ ቅንጅት፣ በከተማዎችና በመንደሮች ግንባታ በመገለጽ ጠቅላላውን ህዝብ እንደ አንድ ማህበረሰብ የሚያስተሳስረው ሳይሆን፣ እዚያው ደቆ የሚያሰቀረው፣ ይበልጥ በደሃና በሃብታም መሀከል ያለው ልዩነት እየጎላ በመሄድ አገሪቱን ለውጭ ኃይሎች አጋልጦ የሚሰጠው ነው። ይህ ፖሊሲ የበለጠ የንግድ ልውውጥ ባህርይ ሲኖረው፣ ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ ኃይል እንዳይዳብር ከማገዱም በላይ፣ በቴክኖሎጂ ላይ የሚመረኮዝና ተወደዳሪነትን ውስጣዊ በማድረግ ካለበት ሁኔታ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለመሸጋገር የሚችል ከበርቴያዊ ኃይል ብቅ እንዳይል የሚያግድ ነው። ባጭሩ ይህ ዐይነቱ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የታቀደ ፖሊሲ ሚኒስተር ዲኤታው ዶ/ር ዕዮብ ተካልኝ እንደሚሉት አገር በቀል የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚታይበት አይሆንም ማለት ነው። በተለይም ደግሞ ዝም ብሎ ማኑፋክቸር ብሎ ባጠቃላይ ከመጥራት በስተቀር ለጠቅላላው ኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ እንደ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው ቴክኖሎጂ በሚለው ላይ ሰፋ ያለ ትንተናና ግንዛቤን የያዘ ፖሊሲ አይደለም። በተለይም ደግሞ፣ ፖሊሲው ውጤታማ የማይሆነው በአገር ቤት ውስጥ ባሉና በውጭው ዓለም በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበትና የተጨመቀ ሃሳብ ሆኖ እንዲወጣ የታቀደ ሳይሆን፣ ከውጭ ኃይሎች ፍላጎት አንፃርና የነሱን ቡራኬ ለማግኘት የተጻፈ ነው ማለት ይችላል።

የኢኮኖሚ ፖሊሲው የቱን ያህል አገር ውስጥ የሚያድግ (Homegrown) ነው!

አዲሱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አገር ቤት ውስጥ የሚበቅልና የሚያድግ ኢኮኖሚ (Homegrown) ነው የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ሳነብ ወይም ስሰማ ግራ ተጋብቼ ነበር፤ እስካሁን ድረስም ሆምግሮውን (Homegrown) ሲባል ምን ለማለት እንደተፈለገ ግልጽ ሊሆንልኝ በፍጹም አልቻለም። ይሁንና ጽንሰ-ሃሳቡን ሊትራሪ ስተረጉመው፣ በእኔ ግንዛቤ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮና ፖሊሲው ረቅቆ ወደ ውጭ እስከወጣበትና ሰው እንዲያውቀው እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በአገሪቱ ምድር የተከናወነውና ዕውን የሆነው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገት አይ በውጭ ኃይል የተደገፈ፣ ወይም ደግሞ ሁሉም ነገር ውጭ አገር አልቆ ደቆ በመርከብ ወይም በአውሮፕላን በመጫን አገር ቤት ውስጥ ከገባና ተግባራዊ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ለጥቅም የዋለ ነው ወደ ሚለው ግንዛቤ ሊወስደን ይችላል። ይህንን ዐይነቱ አተናተን ትቼ ነገሩን ጠጋ ብዬ ስመረምረው የፖሊሲው አውጭዎች ለማለት የፈለጉት በራሳችን ጥረትና በራሳችን በመተማመን (Self reliance) ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የረቀቀ ፖሊሲ ሲሆን፣ ተግባራዊ የምናደርገውም በራሳችን የውስጥ ሀብትና (Resources) የሰው ኃይል በመተማመን ነፃና ብሄራዊ ኢኮኖሚ እንገነባለን እንደማለት ይቆጠራል። ሆምግሮውን የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ከእነዚህ ሁለት አተረጓጎሞች ውጭ በፍጹም ሊሆን አይችልም።

ይሁንና ፖሊሲውን ጠጋ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ ከመሰረታዊ አስተሳሰቡ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ነው። በአንድ በኩል ከውስጥ የፈለቀና በራስ ሀብትና ጥረት ኢኮኖሚውን እናሳድጋለን የሚለውን አስተሳሰብ የሚያስተጋባ ቢመስልም፣ በሌላ ወገን ግን የፖሊሲውን ይዘትና የሚመረኮዝበትን ርዕዮተ-ዓለም በምንመረምርበት ጊዜ በራስ መተማመንና በውስጥ ሀብት መመካትን በፍጹም አያንፀባርቅም። እንዲያውም ከዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በብዙ ሚሊዮን ማይሎች ርቆ የሚገኝ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፖሊሲው ረቆ የዓለም ኮሙኒቲው እንዲያየውና የእነሱን ቡራኬ እንዲያገኝ መደረጉ አገር ቤት ውስጥ ያልበቀለ መሆኑን ያረጋግጣል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ፖሊሲው ሙሉ በሙሉ ኒዎ-ሊበራል ባህርይ ያለውና ለአገር ውስጥ ገበያ ማደግና ለህብረተሰብ ግንባታ የማያመች ነው። እንደሚታወቀው ይህ ፖሊሲ በተለያዩ የላቲን አሜሪካና የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ መቀመቅ ውስጥ የከተታቸውና፣ በአሁኑ ወቅትም ህዝብና መንግስታት ተፋጠው የሚገኙበትን ሁኔታ ያመቻቸ ፖሊሲ ነው። በእኛ አገርም 27 ዓመታት ያህል ተግባራዊ በመሆን ያስከተለውንና በምድር ላይ የሚታየውን ሁኔታ ብዙም ሳንመራመር የምንገነዘበው ሀቅ ነው። ህዝባችንም በየጊዜው ኢኮኖሚው አድጓል ወይም እያደገ ነው ብለው ሲነግሩት፣ የማላየው፣ የማልቀምሰው፣ ካለሁበት ሁኔታ የማያወጣኝና በራሴ እንዳልተማመን የሚያደርግ የኢኮኖሚ ዕድገት የእኔ ዕድገት አይደለም እያለ ነው እቅጩን ሲነግረን የነበረው። ምክንያቱም፣ የሚኖርበት የኑሮ ሁኔታና ከኢኮኖሚ ፖሊሲው ጋር ተጓትተው የመጡ ባህልን አውዳሚ ነገሮች በቁጥር ከሚለካ ነገር ስለሚበልጡ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ ፖሊሲው ረቆ ለዓለም የገንዘብ ድርጅት ከቀረበና ከተጠና በኋላ የገንዘብ ድርጅቱ የ$2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት የተስማማውና የጀርመን መንግስትም በሚመለከተው ሚኒስተሪው አማካይነት አገር ቤት ውስጥ ያድጋል የሚባለውን ኢኮኖሚ መደጎሚያ በማለት የ$300 ሚሊዮን ያደረገው ዕርዳታ የፖሊሲውን ነፃና በአገር ውስጥ ሀብትና በአገር ውስጥ አዋቂዎች እንዳልፈለቀ ያመለክታል። በአራተኛ ደረጃ፣ የኢኮኖሚ ሚኒስተሩ አቶ አህመድ ሺዴ ለቀረበላቸው ቃለ-መጠይቅ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ አሁን አገሪቱ ለውጭ መዋዕለ-ነዋይ ክፍት ስለሆነች የሚፈልግ መጥቶ መዋዕለ-ነዋይ ማፍሰስ ይችላል ብለው የተናገሩት የፖሊሲውን ነፃና አገራዊ ባህርይ የሚያረጋግጥ አይደለም። በተለይም የሳውዲ አረቢያና የካታር ባለሀብቶች አገራችን እየመጡ ኢንቬስት ለማድረግ በማለት የሚያደርጉት ስብሰባና ስምምነት ኢኮኖሚው በውስጡ ኃይል እንዲያድግ የማያደርግና የተስተካከለ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዳይገነባ የሚያደርግ ነው። በዚህ መልክ በውጭ መዋለ-ነዋይ ስም የውጭ ከበርቴዎች ነን የሚሉ በአገራችን ምድር ሽር ጉድ ማለት ሁኔታውን ለዘረፋና ለርካሽ ጉልበት መበዝበዣ የሚያመች ነው። እነዚህ በመዋዕለ-ነዋይ ስም ወደ አገራችን የሚመጡ የገንዘብ ባለሀብቶች በቴክኖሎጂ ዕድገትና በሳይንስ ምርምር ላይ የሚሰማሩ ስለማይሆኑና፣ የአገራችንንም ሀብት ለመቆጣጠር የሚፈልጉ በመሆናቸው የአገር ውስጥ ገበያ እንዳያድግ እንቅፋት ከመሆን በስተቀር ሰፋ ያለ የስራ መስክ የሚያስከፍት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተግባራዊ ሊያደርጉ አይችሉም።  ታዲያ በምን ተዓምር ነው ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አገር ውስጥ ለሚያድግና እራሱን ችሎ ለሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ መሰረት ሊሆን የሚችለው። በአምስተኛ ደረጃ፣ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የፖሊሲው ዋና ዓላማ አንዳች ዐይነት የገበያ ኢኮኖሚን ዕድገት ለማምጣት እንጂ አገሪቱን ዘመናዊ በማድረግ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ላይ በማስመርኮዝ ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት አይደለም። ዋናውና የመጀመሪያው ዓላማም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ድህነትን ከአገራችን ምድር ለማስወገድ አይደለም። የፖሊሲው ዋና ዓላማ በአገራችን ምድር የሚታየውን ችግር በሙሉ የረቀቀው እጅ (Invisible Hand) ይፈታዋል፣ ስለሆነም ሁሉም ነገር የገበያ ኃይሎች ለሚባሉት መለቀቅ አለበት ከሚለው የተሳሳተና በካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ባልታየና በኢምፔሪካል ደረጃ ካልተረጋገጠ ሁኔታ በመነሳት የረቀቀ ነው።

ወደ ፖሊሲው መሰረተ-ሃሳቦች ወይም ሚኒስተር ዲኤታው ምሶሶዎች (Pilars) ናቸው ብለው የሚጠሯቸው፣ በተለይም ማክሮ ኢኮኖሚያዊ የጥገና ለውጥ እናደርጋለን የሚለው ግልጽ አይደለም። በሌላ አነጋገር የኬይንሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ወይንስ የኒዎ-ሊበራሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይሁንና የፖሊሲው አውጭዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻል ሲሉ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅቱን አስተሳሰብ ማስተጋባታቸው እንጂ ኬይንስ እንዳለንና እንዳስተማረን እ.አ.አ በ1930 ዓ.ም በአሜሪካንና በብዙ የካፒታሊስት አገሮች የተከሰተውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ (Economic Depression) ለመፍታት ሲባል መንግስታት መውሰድ የሚገባቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አይደለም። እንደሚታወቀው በጊዜው በሁሉም የካፒታሊስት አገሮች የኢንዱስትሪ ምርት ክንዋኔ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰበት፣ የገንዘብ እንቅስቃሴ ፍሰት ከምርት ክንዋኔ ጋር ባለማያያዙና ኢንዱስትሪዎች የስራ መስክ በመክፈት ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ባለመደረጉና፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት (Hyper Inflation) በመታየቱና የስራ አጡም ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት፣ በኬይንስ ዕምነት ከዚህ ዐይነቱ ቀውስ ለመውጣት መንግስት በቀጥታ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ በመግባት መዋዕለ-ነዋይ ማፍሰስ አለበት። መንግስት በተለይም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ለሚውሉ ነገሮች ላይ (Public goods) መዋዕለ-ነዋይ ሲያፈስ የመጨረሻ መጨረሻ የሚጠቀመው በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰማራው የካፒታሊስት መደብ ነው። ምክንያቱም መንገድ መስሪያ መሳሪያዎች፣ የባቡር ሀዲዶችና ባቡሮች፣ የህንፃ መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቆሶች… ወዘተ. የሚመረቱት በግል ዘርፉ በመሆኑ ነው።  በዚህ መልክ ሰፋ ያለ የስራ መስክም ስለሚከፈት፣ ኢንዱስትሪዎች የመንቀሳቀስና ቴክኖሎጂያቸውን የማሻሻል ዕድል ያገኛሉ። በበተለይም የሰራተኛው የመግዛት ኃይል ስለሚጨምር፣ ካፒታሊስቶች ቴክኖሎጂያቸውን ለማሻሻልና ምርታማነትንም ለማሳደግ ይችላሉ።  በመጀመሪያ በገቢ መጨመርና የፍጆታ ዕቃዎችን በመግዛት የመንግስታት የቀረጥ ገቢ ሲጨምር፣ በሁለተኛ ደረጃ የካፒታሊስቶች ትርፍ ስለሚያድግ የተወሰነውን እንደገና ለመዋዕለ-ነዋይ ስለሚያውሉት ይህ በራሱ አጠቃላይ የሆነ የሀብት ክምችት(Capital accumulation) እንዲፈጠር ያግዛል። በሌላ አነጋገር፣ በኬይንስ ዕምነት በኢኮኖሚው ውስጥ በተለያዩ መሳሪያዎች የመንግስት ጣልቃ ገብነት የግሉን ዘርፍ የማምረት ኃይል የሚያዳክምው ሳይሆን የሚያበረታታውና አጠቃላይ የሆነ የመግዛት ኃይል እንዲጨምር የሚያደርግ ነው። ይህንን የኬይስን ምክር በሌላ መልክ በሂትለር የሚመራው የናዚ መንግስትም ተግባራዊ ሲያደርገው፣ አሜሪካን ደግሞ በፕሬዚደንት ሩዝቤልት የሚመራው መንግስት ለተወሰኑ ሳምንታት ባንኮችን በመዝጋት ቆራጥ እርምጃና ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን በመውሰዱ ኢኮኖሚው ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ከቀውሱ ሊፈወስና ለብዙ ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት ችሏል።

በዚህ ዐይነቱ ፖሊሲና ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ተግባራዊ የሆነውን የመንግስታትን ጣልቃ-ገብ ፖሊሲ (Interventionsist Policy) ስንመለከት ካለመንግስት ጣልቃ ገብነት ኢኮኖሚው ሊያድግ በፍጹም አይችልም። ሎጂኩም ቀላል ነው። ማንኛውም ካፒታሊስት ኢንቬስት ለማድረግ የሚነሳው ትርፍ ለማግኘት እችላለሁ ብሎ ካሰላና የገበያውን ሁኔታ ካጠና በኋላ እንጂ ህዝብን እረዳለሁ፣ ኃላፊነትም አለብኝ ብሎ በመነሳትና በማመን አይደለም። ስለሆነም በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ባይሳተፉ ኖሮ ከዚያ በኋላ የታየው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የስራ-መስክ መከፈት፣ የፈራረሱ ከተማዎችን እንዲገነቡ ማድረግ፣ በንጽሁ ውሃና በመብራት ስርጭትና አቅርቦት፣ በትምህርት ዘርፍ፣ ሀኪም ቤቶችን መገንባትና ለሰፊው ህዝብ ህክምና እንዲዳረስ በማድረግ ባይሳተፉ ኖሮ ኢኮኖሚው በፍጹም ባላደገ ነበር።  ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ፖሊሲ በአገራችን ምድር ውስጥ ሊታለፍ የማይችል ሀቅ ነው። ይህ ዐይነቱ መዋዕለ-ነዋይ በተለይም ለህዝብ ጥቅም በሚውሉ (Public Goods) ነገሮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ የመንግስት መዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ በግል ተሰማርተው የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ ማሽኖችን፣ የሀኪም ቤት ዕቃዎችን፣ የትምህርት ቤት መሳሪያዎችንና መጽሀፎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና ለህዝብ መኖሪያ ቤቶች የሚሆኑ መስሪያ ነገሮችን… ወዘተ. በመጠየቅ ለኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በተለይም መንግስት ለህዝብ የሚሆኑ አገልግሎቶችን ስለሚሰጥ ወይም ስለሚያቀርብ፣ ተጨባጭ ነገሮች ደግሞ የሚመረቱት በግል ኩባንያዎች ስለሆነ ይህ ዐይነቱ ጣልቃ-ገብነት የማባዛት ኃይል (Multiplier effect) አለው። በዚህ መሰረት ነው አሁንም ቢሆን በብዙ የካፒታሊስት አገሮች የሚሰራው። ስለሆነም የዓለም የገንዘበ ድርጅትና (IMF) የአገራችን ኢኮኖሚስቶችና አማካሪዎቻችው እንደሚሉት የመንግስት ጣልቃ-ገብነት የግለሰብ ባለሀብቶችን እንዲገፉ (Crowding Out) በፍጹም አያደርጋቸውም። ይህ ነው እንግዲህ ጥንታዊውና ዋናው የኬይንስ አስተሳሰብና ኢንስቲቱሽናል እኮኖሚስቶች የሚያስተምሩንና የሚነግሩን፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ የሚያስተምረን።

ወደ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አሰተሳሰብና ግፊት ስንመጣ የሚነሱት ከጠቅላላው ሁኔታ ሳይሆን፣ በተለይም የመንግስትን ባጀት፣ የገንዘብን ልውውጥ ጉዳይና የአገር ውስጥ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር ስለመቀነሱ ጉዳይ፣ የመንግስት ሀብቶችን ለግል ኢንቬስተሮች መሸጥና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ሁሉንም ነገር ለገበያ ተዋንያኖች በመልቀቅ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለመሆን ይችላል ከሚለው የተሳሳተና ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ነው። ስለሆነም በእነሱ አመለካከት በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚመረት ምርት ህብረተሰብአዊ ፍላጎትን ያሟላ (Socially necessary product) አያሟላ፣ የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች የመባዛትና የማደግ ባህርይ ይኖራቸው አይኑራቸው፣ ቴክኖሎጂና ሳይንስ የኢንዱስትሪ ክንዋኔን ዕድገት መሰረት ይሁኑ አይሁኑ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ለሰፊው ህዝብ የስራ-መስክ በመከፈት አጠቃላይ የሆነ የፍጆታ ዕቃዎችም ሆነ የአገልግሎት ጥያቄ በማደግ ለጠቅላላው ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታ ይፈጠር አይፈጠር ጉዳያቸው አይደለም። በተለይም ደግሞ ምን ምን ዐይነት ኢንዱስትሪዎች ቢተከሉና፣ በምንስ ዐይነት ቴክኖሎጂዎች ቢደገፉ የተሻለ ማምረት ይቻላል በሚለው ጉዳይና፣ በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የተስተካከለና ውስጠ-ኃይል ያለው የገበያ ኢኮኖሚ ማደግ አለበት ከሚለው ስሌት በፍጹም አይነሱም። ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውም አስተሳሰብ ቁንጽል ስለሆነ በአንድ አገር ውስጥ ሁለ-ገብ በሆነ መልክ ብቻ የሚካሄድ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና የሀብረተሰብ ግንባታ ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መግለጫ እንደሆነ አይ በፍጹም ለመገንዘብ አይፈልጉም፣ አሊያም ደግሞ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኤሊቱን በማሳሳት አንድ አገርና ህዝብ በዘለዓለማዊ ድህነት እንዲታሹና እንዲማቅቁ ያደርጋሉ። ዋና ተግባራቸውም እንደኛ ያሉ አገሮች ለዝንተ-ዓለም ደሀና ደካማ ሆነው እንዲቀሩ ማድረግ ነው።  ስለሆነም ቀላል ፎርሙላቸው ሁሉም ነገር ለገበያው ቢለቀቅ በራሱ ውስጣዊ ኃይል ያድጋል ይሉናል። ከዚህ ከላይ ከቀረበው ሀተታ ስንነሳ በአገራችን በኢኮኖሚና በፋይናንስ መስሪያቤት የረቀቀው ፖሊሲ አንድ በአንድ የዓለም ኮሙኒቲውን ፍላጎት የሚያረካና፣ በአንፃሩ ደግሞ የአገራችን ኢኮኖሚ በውስጥ ኃይሎች አማካይነትና በውስጥ ሀብትና በመንግስት በመደገፍ እንዳያድግ እንቅፋት የሚፈጥር ነው። በመሆኑም የማክሮ ኢኮኖሚው መሻሻልበመሰረቱ ኢኮኖሚውን የሚያሻሽለው ሳይሆን የባሰውኑ የሚያደቀውና ግልጽ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ የሚያደርግ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ እንደኛ ባሉ አገሮች በማክሮ ኢኮኖሚ የሚደገፍ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ መሆን አለበት ሲባል የኪይንስም ሆነ የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የረቀቁት በብዙ እጅ በቴክኖሎጂ መጥቀው ከሄዱ ከካፒታሊስት አገሮች (From the prespective of capitalist society) አንፃር በመነሳት ነው። የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲው በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የማርክሲዝምን የፖለቲካ ኢኮኖሚ በመቃወም የፈለቀ ሲሆን፣ ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ደግሞ በቲዎሪ ደረጃ እየዳበረ የመጣው በ1930ዎቹ ዐመታት ነው።  የኬንይስን ቲዎሪና ፖሊሲ ደግሞ የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክ ቲዎሪን በመቃወም የፈለቀ ሲሆን፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በመሰረቱ በየጊዜው ዝቅና ከፍ የሚል ባህርይ ስላለውና፣ በዚህም ምክንያት አጠቃላይ ቀውስ ስለሚታይ የግዴታ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ካልተደረገበት ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ የሚፈጥር ውስጣዊ ኃይል አለው ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ ነው። በተለይም የኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚ ቲዎሪን ዛሬ ደግሞ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ቲዎሪን ወይም ፖሊሲን ስንመለከት ቲዎሪው ካፒታሊዝም ደረጃ በደረጃ ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚ(Comodity Economy) ወደ ተወሳሰበና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ወደ ተደገፈ ኢኮኖሚ እንዴት እንዳደገ ሎጂካዊ በሆነ የአተናተን ዘዴ በፍጹም አያሳይም። በተጨማሪም በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ምሁሮች ዕምነት አሁንም ቢሆን የካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚ በነፃ ገበያና በውድድር የሚገለጽ ሲሆን፣ ሂደቱም በትናንሽ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች የሚደገፍ ነው ብለው የሚያምኑት። ይህም ማለት፣ ጠቅላላ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ የመንቀሳቅስ ባህርይ የሌለው በመሆኑ (Static)፣ ወደ ትላልቅ ኩባንያዎችና ባንኮች የመለወጥና የማደግ ኃይል የለውም፤ የገበያውን ሂደትና ሀብትን የሚቆጣጠሩ ኦሊጎፖሊስቶች በመባል የሚታወቁ ኩባንያዎችም አይፈጠሩም። በተጨማሪም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለውን መተሳሰርና፣ የፋይናንስ ካፒታል የኢንዱስትሪዎችን ዕድገት እንዴት እንደሚደነግግና፣ ዛሬ ደግሞ የፋይናንስ ካፒታል ራሱን በማግለል ትርፍን በምርት አማካይነት ሳይሆን፣ የአየር በአየር ንግድ (Speculation) ወይም ውድድር ውስጥ በመሳተፍ ትርፍን ለማካበት የሚሯሯጥ መሆኑን በፍጹም አያትትም ወይም በትምህርት ቤት ከሪኩለም ውስጥ አልተካተተም። ባጭሩ፣ ቲዎሪው ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማንበብ የማያስችልና፣ በኢኮኖሚ ሂደት ውስጥ የሚሳተፍ ማንኛውም ግለሰብ አርቆ-አሳቢ ወይም ጥቅሙን የሚያሳድድ ነው ከሚለው ተራ አስተሳሰብ የሚነሳ ነው። ስለሆነም እንደኛ ላለው ኋላ-ቀር ኢኮኖሚ የመተንተኛ መሳሪያ በመሆን ከድህነትና ከረሃብ የሚያላቅቀን አይደለም።

ወደ ሁለተኛው መሰረተ ሃሳብ ወይም ምሶሶ (Pillar) ስንመጣ እንደመጀመሪያው ግልጽ አይደለም። የመዋቅር ለውጥ (Structural reforms) ማለት ምን ማለት ነው? በህብረተሰብ ሳይንስ ውስጥ ሶሻል ትራንስፎርሜሽና ወይንም ስትራክቸራል ቸንጅስ የሚባል ነገር አለ። ይህም ማለት አንድን ህብረተሰብ የሚመለከት አጠቃላይ፣ የፖለቲካ፣ የምርት ግኑኝነትና የሰው በሰው ግኑኝነት፣ የሀብትን ጉዳይ፣ የባህል ጉዳይ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ አንድን ህብረተሰብ ሁለ-ገብ በሆነ መልክ ዘመናዊ ማድረግና፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በአንድ በኩል በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረውና በራሱ ተነሳሽነት ፈጣሪና (Inovative) አምራች ኃይል እንዲሆን ማድረግ፣ ይሁንና ደግሞ የሁሉም የህብረተሰብ አካል መሆኑንና ህልሙንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚችለው ለህብረተሰቡም ሲያስብና የህብረተሰቡም አካል መሆኑን ሲሰማው ነው። ከዚህ በተረፈ የመንግስትና የፖለቲካን ሚናና ጠቅላላውን ሁኔታ ስለማሻሻሉ ጉዳይና፣ ደረጃ በደረጃ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች… ወዘተ. እነዚህ ነገሮች በአንድ ላይ ሲደመሩ ህብረተሰብአዊ ለውጥን ወይም ስትራክቸራል ቼንጅን ያስከትላሉ። ይህ ዐይነቱ የመዋቅር ለውጥ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ወይም ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን በሂደት ከብዙ ዐመታት በኋላ፣ በተለይም የአስተሳሰብ ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። የሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና መዳበር የብዙ መቶ ዐመታት ክንዋኔን ስለሚጠይቅ እንደዚሁ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚመጣ ለውጥ ቀስ በቀስ የሚተገበርና ሰውም እየተለማመደው የሚመጣው ነው። ይህም ማለት አንድን ህብረተሰብ በማስገደድ ብቻ የመዋቅርና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት በፍጹም አይቻልም።  ስለሆነም ህብረተሰብአዊ ወይንም የመዋቅር ለውጥ እንዳይመጣ እንቅፋቶች ይኖራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ በተለይም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስታተስ ያላቸውና በተቀረው ህዝብ ልፋት የሚኖሩ ስታተሳቸው እንዳይለወጥ ይፈልጋሉ፤ አጥብቀውም ይታገላሉ። በተለይም የርዕዮተ-ዓለም መሳሪያ ካላቸው እሱን በመጠቀምና ቅስቀሳ በማድረግ ለውጥ ከመጣ ወደ ጨለማ ሁኔታ ታመራላችሁ በማለት ለሰፊው ህዝብና ለአገር የሚጠቅም የተሻለ ሁኔታ እንዳይፈጠር ህዝብን ውዝንብር ውስጥ ይከቱታል። በዚያው መጠንም ለተሻለ ሁኔታ የሚታገለውን የህብረተሰብ ክፍል አይ ስሙን ያጠፋሉ፣ አሊያም ደግሞ በአንዳች መንገድ እንዲወገድ ያደርጋሉ። በዚህ መልክ በተለይም ተቀባይነትን ካገኘና የገዢ መደቦችን ጥቅም የሚያስጠብቀውን ዕውቀት (Conventional Wisdom) በመቃወምና ሰፊውን ህዝብ አዕምሮውን ክፍት በማድረግ ጥያቄ በመጠየቅና ማንነቱን እንዲገነዘብ ያስተምሩ የነበሩትን እንደሶክራተስ የመሳሰሉትን የአምላኮችን ህግ የሚጥስ የውሸት ትምህርት ለወጣቱ ያስተምራል በመባል ተከሶ የመጨረሻ መጨረሻ መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት ተደርጓል። በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ በአውሮፓ ምድር ውስጥም እነቡሩኖ ጊዮርዳኖ የመሳሰሉት ቄሶች፣ ገጣሚዎች፣ ፈላስፋዎችና የአስትሮኖሚ ምሁራን እንዲቃጠሉ የተደረገውና፣ ጋሊሌዮ ጋሊሌዪ ወደ እስር ቤት የተወረወሩት በጊዜው የነገሰውንና፣ በተለይም ባልተማረው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውን የካቶሊክን ቀኖና በመቃወማቸውና ለሳይንስና መንፈስን ለሚያድሰው ለትክክለኛው ፍልስፍና በመታገላቸው ነው።

ነገሩን እዚህ ላይ ለማሳጠር የግሪክ ፈላስፎችም ሆነ የኋላ ኋላ የሬናሳንስ ምሁራን ለመዋቅር ለውጥ ከመታገላቸው በፊት ለመዋቅር ለውጥ እንቅፋት የሆነውን ርዕዮተ-ዓለምና በጊዜው የተስፋፋውንና ሰፊውን ህዝብ በማሳሳት የገዢ መደቦችን የጭቆና ስርዓት ዘለዓለማዊ የሚያደርገውን የውሸት ዕውቀት (Conventional Wisdom) መታገልና፣ በተለይም ወጣቱን የሚያሳስተውን አስተሳሰብ አሽቀንጥረው በመጣል ዕውነተኛ ዕውቀትን ማስጨበጥ ነበረባቸው። ይህም ማለት የመዋቅር መስተካከያ ወይም መሻሻል ከመደረጉ በፊት የጭንቅላት አብዮት መካሄድ እንዳለበት ለፈላስፋዎች ግልጽ ነበር። ይህ ዐይነቱ ትግል በተለይም ግሎባል ካፒታሊዝም አይሎ በወጣበት ዘመንና የሰውን ልጅ ዕድል በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ብቻ በመከለል እንደኛ ያሉ አገሮችን ዘለዓለማዊ ተበዝባዥና ጥሬ-ሀብት አቅራቢ ሆነው እንዲቀሩ ለማድረግ በሚሯሯጥበት ዘመን ትግሉ እጅግ ውስብሰብ የሆነና የጠለቀ ጥናትንና የብዙ ምሁራንን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። ከዚህ ስንነሳ የመዋቅር ለውጥ ያስፈልጋል ወይም ይደረጋል ተብሎ በሚኒስተር ዲኤታው በፓወር ፖይንት የቀረበው ተግባራዊ የማይሆነው መሰረታዊ የሆነውን የጭንቅላትን ተሃድሶ ያላከተተ በመሆኑና፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ መካሄድ ያለበትን የከተማዎችንና የመንደሮችን ግንባታና፣ በተጨማሪም የትናንሽና የማዕከለኛ፣ እንዲሁም የዕደ-ጥበበብ ሙያዎችንና ኢንዱትሪዎችን መትከል አስፈላጊነት ያላካተተ በመሆኑ ነው።

ይሁንና የኒዎ-ሊበራል ወይም የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ስለመዋቅር መሻሻል ሲያወሩ ምን ማለታቸው እንደሆነ ጠጋ ብሎ መመልከቱ እነሱ በሚያስፋፉት የተሳሳተ አስተሳሰብና ስለዕውነተኛው የመዋቅር ለውጥ ያለውን ልዩነት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች አንድ አገር የመዋቅር መሻሻል ማድረግ አለባት ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?  ስለመዋቅር መሻሻል ሲያወሩ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት ማለታቸው ነው ወይ? ወይስ ሌላ የማይጨበጥ፣ የማይታይና በቀላሉ ሊተነተን የማይችል ነገር ነው የሚነግሩን?  የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የመዋቅር መሻሻል ያስፈልጋል ሲሉ በአውሮፓ ምድር፣ በተለይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የበላይነትን መቀዳጀት ከጀመረበት ከ1970ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በመዋቅር ለውጥ ሳቢያ የተስፋፋ የተወላገደ አስተሳሰብ አለ። ይኸውም በተለይም የወዝ አደሩን የመደራጀትና የመደራደር አቅም ማዳከም፤ አምራቾች በፈለጉት ጊዜ ሰራተኛውን የማባረር መብት እንዲኖራቸው ማድረግ። ሰራተኛውን በርካሽ ደሞዝ ማሰራትና፣ ለጊዜው የማያስፈልገውን ደግሞ በርካሽ ደሞዝ ለሌላ ኩባንያ ማከራየት… ወዘተ.፣ እነዚህ የመሳሰሉትና የመንግስትን ሚና በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደ መዋቅር ለውጥ አድርገው ይመለከታሉ፤ ይህንንም ዘመናዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ብለው ብዙ ኤሊቶችን ያሳስታሉ። በዚህ መልክ የተስፋፋው የተሳሳተ የመዋቅር መስተካከያ ፅንሰ-ሃሳብ የመጨረሻ መጨረሻ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዕይታዎች (Implications) አለው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሰበክ እንደኛ አገሮች ያሉ መሰረተ-ሃሳቡን በሚገባ ሳይረዱ ኢኮኖሚው እንዲዳከምና የባስውኑ በውጭ ኃይሎች ጥገኛ እንዲሆን በማድረግ የህዝብ ነፃነት፣ በተለይም ደግሞ ሰራተኛው በሙያ ማህበር እንዳይደራጅና በእኩል ደረጃ ስለስራው ቦታና ስለደሞዙ እንዳይደራደር ይደረጋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሰራተኛው በቂ ደሞዝ ስለማይከፈለው እራሱ እንደገዢና ተጠቃሚ በመሆን ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋፅዖ እንዳያበረክት ይደረጋል። በኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገት ውስጥ በቂ ጠያቂ(Effective Demand) የሚባል ነገር አለ። በአንድ አገር ውስጥ የሚመረት ምርት በራሱ በአምራቹና በተቀረው ህዝብ እየተገዛ ለጥቅም የማይውል ከሆነ በአጠቃላይ ሲታይ፣ በአንድ በኩል አምራቹ በየጊዜው የማምረት ኃይሉን አያሳድግም፣ ለመወዳደር የሚያስችለውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል የምርት ዋጋን በመቀነስ ለተጠቃሚው ደግሞ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ የመሸጥ ዕድል አያገኝም። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የሰራተኛው ደሞዝ በየጊዜው ካላደገና ሰራተኛውም ራሱ ያመረተውን ምርት ገዝቶ የመጠቀም ዕድል ካላገኘ በገንዘብና በምርት መሀከል፣ እንዲሁም ገንዘብ ወደ ካፒታል መለወጥና ኢንዱስትሪዎችን በመትከልና በማስፋፋት መሀከል የሚኖረው ግኑኝነት ይቋረጣል። ባጭሩ፣ ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ በፍጥነት ካልተሽከረከረና ወደ መዋዕለ-ነዋይነት የመለወጥ ዕድል ካልገጠመው ይህ በራሱ የዋጋ ግሽበትን ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለው፣ ሰፋ ያለ የካፒታል ክምች እንዳይፈጠር ያደርጋል። ከዚህ ትንተና ስንነሳ በሚኒስተር ዲኤታው የቀረበው የመዋቅር ማሻሻያ ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራል ባህርይ ያለው በመሆኑ የአገር ውስጥ ገበያ እንዳይስፋፋ ያግዳል፤ የአገር ውስጥ ገበያ በማያድግበት አገር ደግሞ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ከዕውነተኛ ሳይንስ ሃሳብ ስንነሳ ሁለቱ ምሶሶዎች ወይም መሰረተ-ሃሳቦች መዋቅር በሚለው ሃሳብ ውስጥ በመጠቃለል ሁለ-ገብ የሆነ መሰረታዊና የመዋቅር ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል በሚለው ቢተካ ኖሮ ነገሩን ማሳጠር ይቻል ነበር።  በሌላ አነጋገር፥ ማክሮና መስክ ተብለው የቀረቡት ምሶሶዎች የጠቅላላው መዋቅር አካል ሆነው መታየት ያለባቸው ጉዳዮች እንጂ ተነጥለው በመታየት መሻሻል የሚገባቸው አይደሉም። አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚመጣው ነገሮችን በተናጠል በማየት ሳይሆን አንዱ በሌላው ላይ ያለውን ተፅዕኖ በመመርመርና ሁለ-ገብ ፖሊሲ በመከተል ብቻ ነው።

ከዚህ በተረፈ ሌሎች የሚነሱ መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። ፖሊሲው ለአዲስ አበባና ለአካባቢው ወይንስ ሁሉንም ክልሎች ወይም ክፍለ-ሀገራት ይመለከታል ወይ? በፖሊሲው አወጣጥ ውስጥ የየክልሎቹ አስተዳዳሪዎች ሚና ምንድነው? በየክልሎችስ ውስጥ ምን ምን ዕይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ? የየክልሉ አስተዳዳሪዎች የየራሳቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት በየአካባቢያቸው ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ?  የሰውን ጉልበትና የተፈጥሮ-ሀብትን ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ተቋማትን የመገንባት ችሎታ አላቸው ወይ? ከዚህ በተረፈ በተለይም ሀብት ያለው ኢንዱስትሪዎችን እንዲተክል የሚገፋፉ ወይም የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች አሏቸው ወይ? ባጭሩ በየአካባቢው ንግድና ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ምክርና ትምህርት የሚሰጡ እንደ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች አሉ ወይ? እነዚህ ነገሮች በሌሉበትና የየክልሎች ሚና በማይታወቅበት አገር ፖሊሲው ስለብሄራዊ ኢኮኖሚ የሚያወራ ሳይሆን ስለ አንድ ቦታ ብቻ ነው የሚያወራው ብሎ መደምደም ይቻላል። ስለሆነም የኢኮኖሚ ፖሊሲው አገራዊና ብሄራዊ ባህርይ የሌለውና ሰፋ ያለና ግልጽ የሆነ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ የገበያ ኢኮኖሚ እንዲገነባ የሚያግዝ አይደለም ።

ይህንን ትተን ወደ ሌሎች ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለአገር ግንባታ በጣም አስፈላጊ ወደ ሆኑ ጉዳዮች ስንመጣ መንግስትም ሆነ የሚመለከተው መስሪያ ቤት ያቀረቡት ሀተታ በፍጹም የለም። በተለይም ግልጽ የሆነ ፖለቲካና ሰላም መኖር ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። እንደሚታወቀው ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከጨበጡ ጀምሮ ከዚያ በፊት የተዘረጋውን ግኑኝነትና 28 ዐመት በሙሉ በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍን የተቀነባበረውን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ በመጠቀም አለመረጋጋት አለ። በተለይም ጊዜው የኛ ነው ብለው እዚህና እዚያ የሚሯሯጡና የጥላቻ መንፈስ የሚነዙ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በተለይም በኦሮሚያ ክልልና በጋምቤላ ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍን እያደረጉና፣ በተጨባጭ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ ከፍተኛ መሰናክል ፈጥረዋል፤ እየፈጠሩም ነው። ሰሞኑን የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ባደረገው ስብሰባ ላይ እንደ ዋና አጀንዳ የተወያየበት በአገሪቱ ውስጥ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታና የሰላም እጦት ችግር ነው። በተለይም ማንኛውም ዜጋ ወይም በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ የሚፈልግ ሰው ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለመንቀሳቀስም ሆነ ከአካባቢው አልፎ ሌላ ክልል ኢንቬስት ለማድረግ ቢፈልግ እርግጠኝነት እንዲሰማው ይፈልጋል። የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ደግሞ ኤንቬስተሮች መጥተው ሀብታቸውን እንዲያፈሱና የስራ-መስክ እንዲከፍቱ የማያበረታቱና ለዚህም የሚስማማ ህግ ከሌላቸው በአገሪቱ ውስጥ የመዋዕለ-ነዋይም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ይቀዘቅዛል። ይህንን በመረዳት ምክር ቤቱ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስን ጉዳይ፣ የፖለቲካ መረጋጋትን ሁኔታ፣ የጠንካራ መንግስትንና የህግ የበላይነትን አስፈላጊነት፣ በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ጉዳይና፣ እንዲሁም በዲሞክራሲና በአገራዊ ማንነት ባሉት ግኑኝነቶች ተወያይቷል።  በተለይም በንግድና በተለያዩ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች ውስጥ የተሰማራው እንደዚህ ዐይነት እሮሮ የሚያሰማና በጭንቀት ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ስለጥገና ለውጥና ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም ማውራት አይቻልም። ለአገሬው ከበርቴ ቅድሚያ ከመስጠትና እንክብካቤ ከማድረግ ይልቅ አንዳንድ የክልል መሪዎች ሆን ብለው የያዙት የውጭ ከበርቴዎች መጥተው ዘረፋ እንዲያደርጉ ነው ሁኔታውን የሚያመቻቹትና የአገር እሴቶች እንዲበጣጠሱ የሚያደርጉት። ይህንን ጉዳይ በተለይም የማዕከላዊው መንግስት ከየክልል አስተዳዳሪዎች ጋር በመነጋገር በየክልሉ የሰለጠነ ስራ እንዲሰራ አስፈላጊውን የአስተዳደር ተቋም እንዲዘረጋ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። የየክልል አስተዳዳሪዎችም በየአካባቢያቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱና የስራ-መስክም እንዲከፈት የሚፈልጉ ከሆነ ሰላምና መረጋጋት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ለከተማዎችና ለመንደሮች ማበብ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ መገንዘብ አለባቸው። ስለሆነም የየክልል አስተዳዳሪዎች አንደኛው ከሌላው በልጦ ለመገኘት ሲሉ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሚሊሺያኖች ከማሰልጠንና ጠቅላላ አገሪቱን ወደ ጦር ቀጠና ከመለወጥ ይልቅ ለዚያ የሚፈሰውን ገንዘብ ለተቋማት መገንቢያ፣ ለመንገድና ለከተማዎች ግንባታ፣ እንዲሁም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲተከሉ ለመደጎሚያ ቢውሉ በየአካባቢው ተዓምር መስራት በተቻለ ነበር። ከብዙ ሺሆችና ወታደሮች ይልቅ ዕውቀት፣ የሰለጠኑ ተቋማትና ሰፋ ያሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የአንድን አገር ደህንነት የመጠበቅና ስላምን የማስፈን ኃይል አላቸው። በሌላ ወገን ግን እየሰለጠነ እንዲዘዋወር የሚደረግና ህዝብን የሚያስፈራራ ፖሊሲና ሚሊሺያ አምራች ኃይል ስላልሆነ በራሱ ለአንድ አገር ዕድገት ምንም ዐይነት አስተዋፅዖ አያበረክትም። ፀጥታ ጠባቂ ፖሊስ አያስፈልግም ለማለት ሳይሆን አገሪቱና ክልሎች ከሚችሉት በላይ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሚሊሺያኖችንና ፖሊሶችን ማሰልጠንና ማሰማራት ኢኮኖሚውን ይጎዳል፤ አገር እንዳይሰለጥን ያግዳል። ክልሎችና በአጠቃላይ ሲታይ አገሪቱ የሚያስፈልጓቸው ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች፣ ደራሲዎች፣ ሰዓሊዎችና ጥሩ ጥሩ ዘፋኞችና የሰለጠኑ የባህል የማዕከል ቦታዎች እንጂ ወደ ማዕከለኛው ዘመን የሚጎትተንን ያልሰለጠነ ስራ አይደለም። ስለለውጥና ስለዘመናዊነት ስናውራ እነዚህን ነገሮች በጭንቅላታችን ውስጥ መቋጠር አለብን።

ባጭሩ መንግስት ፖሊሲውን ሲነድፍ እነዚህንና ሌሎች ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት ያሰበበት አይመስልም። እንደሚታወቀው ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለንግድ እንቅስቃሴ በአንድ አገር ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት መኖር አለበት። በሁሉም አካባቢዎች ስላም መስፈን አለባቸው። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚሳተፉት ግለሰቦችና ድርጅቶች ሊበሉና ሊጠጡ፣ እንደዚሁም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት ገበሬው ሲያመርትና የተመረተውም ገበያ ላይ መጥቶ ሲሸጥ ብቻ ነው። እንደዚሁም ሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚዳብሩትና ለሰፊው ህዝብና ፖለቲከኛ ነኝ ለሚለው አገልግሎት መስጠት የሚችሉት በአንድ አገር ውስጥ የተሟላ ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው። በተለይም በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት በአንድ አገር ውስጥ ማንኛውም ዐይነት ምርት እንዴት እንደሚመረትና የአምራቹንም የኑሮ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማወቅ አለበት። ሌላው ለፍቶ ጥሮ ያቀረበውን ከተመገቡ በኋላ የተደራጀ ብጥብጥ ማስነሳትና በህዝብ ዘንድ አለመተማመን እንዲፈጠር ማድረግ የነገሮችን እርስ በእርስ መተሳሰር አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ኃላፊነት የጎደለውም ተግባር እንደመፈጸም ይቆጠራል። ስለሆነም በፖለቲካ ክንዋኔ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል ሰው ሁሉ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊናና የሞራል ብቃትነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በህዝብ ዘንድ መተማመን እንዲኖር በየቦታው ስናይፐር ይዘው የሚዞሩትንና በፖለቲካ ስም ወደ ብጥበጣ ዓለም የተሰማሩትን ማገድ ያስፈልጋል። አገር ታሪክ የሚሰራበት ስለሆነ አንድ ህዝብ ታሪክን ሊሰራ የሚችለው የመንፈስ ዕረፍት ሲኖረው ብቻ ነው። ስለሆነም መንግስት የሚባለው አካልና የየክልል አስተዳዳሪዎች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ህይወትና በስነ-ልቦና መሀከል ያለውን ግኑኝነት በመገንዘብ ለሰላም አጥብቀው መስራት አለባቸው። ይህ ብቻ ሲሆን ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለአገር ግንባታ ማውራት ይቻላል።

ከውጭ የሚመጡ ኢንቬስተሮች የአንድን አገር ኢኮኖሚ ማሳደግ ይችላሉ ወይ!

አገር በቀል በመባል የሚታወቀው ፖሊሲ ሲነደፍና ሲታወጅ ዋና ዓላማውም የውጭ ኢንቬስተሮችን ለመሳብ ያስችላል በሚል ነው። በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የውጭ መዋዕለ-ነዋይን (Direct investment) በሚመለከት የተሳሳተ አመለካከትና ግንዛቤ አለ። ይህ ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችም ሆኑ የአገራችን መንግስታት ስለአገር ግንባታና፣ በተለይም ደግሞ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተሳሳተ ግምት አላቸው። ምክንያቱም የሚንቀሳቀሱበት የምሁር መሰረት በጣም የሳሳና ሰፋ ያለና የጠነከረ የሲቭል ማህበራት ስለሌለ ነው።

ኢኮኖሚ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን የያዘ ሲሆን፣ እነሱም ምርት (Production)፣ የደሞዝ ክፍፍል(Income Distribution) ፍጆታ(Consumption) ናቸው። ምርት ደግሞ በሶስት መሰረታዊ ነገሮች ላይ የሚመረኮዝ ነው። እነዚህም፣ ማሽን፣ ኃይልና (Energy) የሰው ጉልበት ናቸው።፡ እነዚህን ሶስት ነገሮች ለማንቀሳቀስ ደግሞ የግዴታ የጥሬ-ሀብትና የእርሻ መሬት መኖር አለባቸው። እነዚህን ነገሮች ያላካተተና በእነዚህ ነገሮች መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት ከሌለ ስለ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገት በፍጹም ማውራት አይቻልም። ስለሆነም ከውጭ ስለሚመጣው መዋዕለ-ነዋይ በሚወራበት ጊዜ ጽንሰ-ሃሳቡ ከእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ተነጥሎ መታየት የለበትም።

በአጠቃላይ ሲታይ መዋዕለ-ነዋይ (Investment) የሚለው ትልቅ የኢኮኖሚ ጽንሰ-ሃሳብ የአምራችን መንፈስና ተሰጥዖ (Entrepreneurial Spirit) የሚጠይቅና ክሽፈትንም (Risk) ለመውሰድ ዝግጁ የሆነ መሆን አለበት። መዋዕለ- ነዋይ የተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ሲኖሩት፣ ሌሎች ቅድመ-ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ አንድ ካፒታሊስት መዋዕለ-ነዋዩን ሲያፈስና ሲያመርት ምርቱ በቂ ጠያቂና ገበያ ካገኘ ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችን በመትከል የምርቱን ክንውን ያስፋፋል። ተጨማሪም የስራ-መስክ ይከፍታል። ተወዳዳሪ ከመጣበት ደግሞ የምርቱን ጥራትና ዐይነት በመለወጥ ከገበያው ላለመውጣት ይታገላል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የተሻሉና የማምረቻ ዋጋን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል ተወዳዳሪነቱን ያረጋግጣል። ከዚህም በላይ የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ተለዋዋጭ ዕቃዎችንና ማሽኖችን የሚያቀርቡላቸው ወይም የሚሸጡላቸው ኢንዱስትሪዎች አሉ። ከእነሱ ጋር ስለሚያያዙ የግዴታ ምርታቸውን ሸጠው ከሚያገኙት ትርፍ የተወሰነው ወደ እነሱ ጋ ይፈሳል። በዚህ መልክ የሀብት ስርጭትና አጠቃላይ የሀብት ክምችት ይፈጠራል። ይህ ዐይነቱ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ጤናማውና ለአንድ አገር ብሄራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት የሚጥልና አገርን የሚያጠነክርና ህዝብንም የሚያስተሳስር ነው።

ከውጭ የሚመጣውን መዋዕለ-ነዋይ በምንመለከትበት ጊዜና የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ ከውጭ የሚመጣ መዋዕለ-ነዋይ ከላይ የተዘረዘረውን የመዋዕለ-ነዋይ ህግ የማይከተል ነው። በመሆኑም በየአገሮች ውስጥ የተስተካከለና ሚዛናዊ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም አይታይም። አንድ ከውጭ የሚመጣ ከበርቴ ነኝ የሚልና በመዋዕለ-ነዋይ ሊሳተፍ የሚፈልግ እንደኛ አገር የመሳሰሉት ጋ የሚመጣው ከራሱ ንጹህ ፍላጎትና ምኞት ብቻ በመነሳት እንጂ የአገር ውስጥን ገበያ አሳድጋለህ፣ ሰፋ ያለ የስራ-መስክም እከፍታለሁ ብሎ በማሰብ አይደለም። ይህንን ለማድረግ የእሱን የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ እንቅፋት ይሆናሉ፣ የሚፈልገውንም ትርፍ እንዳያገኝ ያግዱታል የሚባሉ ነገሮች በሙሉ ከመጀመሪያውኑ መነሳት አለባቸው። እነዚህም፣ 1ኛ) ሰራተኛው በሙያ ማህበር መደራጀት የለበትም፣ 2ኛ) በዝቅተኛ ደሞዝ መስራት አለበት፣ 3ኛ) ከቀረጥ ነፃ መሆን አለበት፣ 4ኛ) ትርፉን ወደ ውጭ የማስተላለፍ መብት እንዲኖረው ይፈልጋል። ይህም ማለት የተወሰነውን ትርፉን አገር ውስጥ እንደገና ኢንቬስት በማድረግ የስራ-መስክ አይከፍትም፤ ለኢኮኖሚው ዕድገትም አጋዥ አይሆንም። 5ኛ) የአካባቢና የሶሻል ስታንደርዶች መነሳት አለባቸው። እነዚህና ሌሎች የእሱን ጥቅም የሚቀናቀኑ ነገሮች ሲነሱ ብቻ ነው መጥቶ መዋዕለ-ነዋዩን የሚያፈሰው። ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ መልክ ከውጭ የሚመጣ መዋዕለ-ነዋይ አገር ቤት ውስጥ ከሚካሄደው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ግኑኝነት የለውም። ይህም ማለት ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስፈልጉ በተለያየ መልክ የሚገለጹ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነቶች(Linkages) በውጭ መዋዕለ-ነዋይ አማካይነት ተግባራዊ አይሆኑም ማለት ነው።  በሌላ አነጋገር የውጭ ኢንቬስተር የሚባለው ወደ አገር ውስጥ የሚመጣው የአንድን አገር ሀብት ለመዝረፍና ወደ ውጭ ለማስወጣት እንጂ የአገሩ ከበርቴ አካል በመሆን የቴክኖሎጂ መሻሻልን በማድረግ የአገርን ኢኮኖሚ በፀና መሰረት ላይ እንዲገነባ ማድረግ አይደለም።

ከዚህ ስንነሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመባል በየቦታው የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች ከላይ የተዘረዘሩትን የኢኮኖሚ ህጎችና መሰረተ-ሃሳቦች በፍጹም የሚያሟሉ አይደሉም። እንደምንከታተለው በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚመረቱት ምርቶች ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ያለመያያዛቸው ብቻ ሳይሆን፣ ምርቶችም ለውጭ ገበያ ተብለው የሚመረቱ ናቸው። እዚያ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት ወጣት ሴቶችና ወንዶች እራሳቸውን ለማኖር የሚያስፈልጋቸውን የወር ደሞዝ የማግኘት ዕድል የላቸውም። በሌላ አነጋገር፣ የባርያ ደሞዝ እየተከፈላቸው ነው የሚሰሩት። ከዚህም በላይ የመጸዳጃ ቤት እንኳ ለመሄድ እየተጨነቁ ነው የሚሄዱት። ግልምጫና ስድብ ይደርስባቸዋል። ይህ እሮሮ በየጊዜው ይሰማል። ይህንን አስመልክቶ ለመንግስት አቤቱታ ሲቀርብ፣ በተለይም የዶ/ር አቢይ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አርከበ ኦቁበይ ሲጠየቁ የመለሱት መልስ፣ ዶሞዝ እንዲጨመር ካደረግን የውጭ ኢንቬስተሮች አይመጡም የሚል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አነስተኛ ደሞዝ ለመስራት የማይፈልግና ተቀጥሮም ይሰራ የነበረ ስራውን ለቆ በሚሄድበት ጊዜ አሰሪዎች የሰራተኛ እጥረት እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ይህም የሚያሳየው መንግስትም ሆነ አማካሪው በቀጥታ የሚሰሩት ለውጭ ከበርቴዎች እንጅ የአገራችን ኢኮኖሚ እንዲያድግ አይደለም። ይህ ዐይነቱ አባባል ደግሞ የኢኮኖሚ ሳይንስን ህግ የሚጥስና የአንድ አገር ኢኮኖሚ በምን መልክ ማደግ እንዳለበት ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።  ይህንን ለመረዳት ከላይ የጠቀስኳቸውን ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ማለትም፣ ምርት (Production)፣ የገቢ ክፍፍልና (Distribution) ፍጆታ (Consumption) በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያላቸውን ሚና ጠጋ ብለን እንመልከት።

በመጀመሪያ ማንኛውም አገር የብዙ ውጣ ውረዶች ውጤት ስለሆነ የራሱ የሆነ ነፃነት አለው። ነፃነቱን ለማረጋገጥና ህዝቡንም ለማስከበር ከፈለገ አንድ መንግስት ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት። አንድን ጠንካራ አገር ለመገንባት ደግሞ መሰረታዊ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ መሰረተ ሃሳቦችን በጭንቅላት ውስጥ መቋጠር ያስፈልጋል። የአንድ አገር ህዝብ ሊተሳሰርና እያንዳንዱ ዜጋም አገሩን አገሬ ነው ብሎ ሊጠራ የሚችለው የሚመረኮዝበት ሰፊ የኢኮኖሚ መሰረት ሲኖረው ብቻ ነው። ስለሆነም አንድ ህዝብና አንድ አገር ሊተሳሰሩና ሊጠናከሩ የሚችሉት ከከተማዎችና ከመመላለሻ መንገዶችና መገናኛ መስመሮች ባሻገር በተለይም ሶስቱም የኢኮኖሚ መስኮች፣ ማለትም የኢንዱስትሪው፣ የእርሻውና የአገልግሎቱ መስኮች እንደሰውነታችን በብዙ ሚሊዮን ነርቦች እንደተሳሰሩና በተለያዩ የሰውነት ኦርጋኖች በስራ ክፍፍል መልክ እንደሚገለጸው የአንድ አገር ኢኮኖሚም እንደዚሁ መተሳሰርና በየጊዜው መሻሻል አለበት። ይህ ብቻ ሲሆን የአንድ አገር ኢኮኖሚ በቁጥር እያደገ ለሚመጣ ህዝብ የስራ መስክ መክፈትና በቂ ምግብና ውሃ ማዘጋጀት ይችላል። ስለሆነም በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ ምርት፣ የገቢ ክፍፍልና ፍጆታ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። በሌላ አነጋገር፣ የሚመረተውን ምርት ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛና የተቀረው ህዝብ ገዝተው የመጠቀም ኃይል እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በቂ ደሞዝ እንዲከፈላቸው ያስፈልጋል። ከቤት ኪራይ፣ ከጤና፣ ከመብራትና ከውሃና ከሌሎች ነገሮች የተረፋቸውን የተወሰነውን ገንዘብ ምግብና ልብስ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ይጠቀሙበታል። ይህም ማለት ከሚያገኙት ገቢ አብዛኛው መልሶ ወደ ኢንዱስትሪዎችና ወደ ንግድ መስኩ ይፈሳል። በዚሀ መልክ በአምራቹና በተጠቃሚው ህዝብ መሀከል ግኑኝነት ይፈጠራል ማለት ነው። ይህ ቀላል የኢኮኖሚ ህግ ነው።

ማንኛውም አገር የተለያዩ ምርቶችን ያመርታል። የምርት ጥራትና በብዛት መመረት በዕውቀትና ተግባራዊ በሚሆነው ቴክኖሎጂ የሚወሰን ነው። ስለሆነም አንድ መንግስትና የተማረ ኃይል ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው የሰውን ፍላጎት የሚያሟሉ በአገሩ ውስጥ በቂና የተለያዩ ምርቶች እንዲመረቱ ማድረግ ነው። የሚመረቱት ምርቶች በቅድሚያ ለውጭ ገበያ ተብለው ሳይሆን የአገሬውን ህዝብ ለመመገብና የአገር ውስጥ ገበያን ለማሳደግ ነው። በየመስኮች ውስጥ የሚመረተው ምርት ደግሞ በነፃ የሚከፋፈል ስለማይሆን በየመስኩ ተሰማርቶ የሚሰራው ሰራተኛ ያመረተውን ምርት ገዝቶ ለመጠቀም ተመጣጣኝ ደሞዝ ማግኘት አለበት። የሰራተኛው ደሞዝ ደግሞ ማደግ የሚችለው ኢንዱስትሪዎችና የእርሻ ማሳዎች ምርታማ ሲሆኑና፣ የሚመረቱት ምርቶች በፋብሪካ ውስጥ ሲፈበረኩ ወይም ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ሲለወጡ ብቻ ነው። ሰራተኛውና የተቀረው ህዝብ በአገር ውስጥ የሚመረተውን ማንኛውም ዐይነት ምርት ገዝቶ የመጠቀም ኃይል ካለው ኢንዱስትሪዎችና የእርሻ መስኩና፣ እንዲሁም የንግድ ዘርፉ ያድጋሉ፤ ይተሳሰራሉ። ይህ ዐይነቱ በምርት፣ በደሞዝ ክፍፍልና በፍጆታ መሀከል ያለው ግኑኝነት ጠቅላላውን ኢኮኖሚ ሊያሳድገው ይችላል። ከዚህ ግልጽ ሀተታ ስንነሳ ከውጭ የሚመጣው መዋዕለ-ነዋይ ይህን ዐይነቱን የሀብት ክምችትና ጠንካራ የሆነ የአገር ውስጥ ገበያ የመፍጠር ኃይል የለውም። የአገር ውስጥ ገበያን ማሳደግና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት አስተዋፅዖ የሌለው በኢንቬስትሜንት ስም ከውጭ የሚመጣ ባለሀብታም የግዴታ በሀብት ዘረፋ ላይ ነው የሚሰማራው። በጥልቀት የሚያስብና ስለኢኮኖሚ ህግ የሚያውቅና አገር ወዳድ ነኝ የሚል መንግስት ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ አንድን አገር የሚያስበዘብዝና ህዝቡን ለዝንተ-ዓለም ደሃ አድርጎ የሚያስቀር በኢንቬስትሜንት ስም ከውጭ የሚመጣን ባለሀብታም ፈቃድ መስጠት የለበትም። የውጭ ባለሀብቶች ነን የሚሉ አገር ቤት በመምጣት አገር እንዲያተራምሱ የመፍቀድ መብትም የለውም። አንድ አገርና በአገር ውስጥ የሚገኝ መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ-ሀብቶችና የጥሬ-ሀብትም የጠቅላላው ህዝብ ሀብት እንደመሆናቸው መጠን አንድ አገዛዝ በራሱ ፈቃድ ዝም ብሎ በመነሳትና የንግድ ስምምነት በማድረግ አገርን የማስበዝበዝ መብት የለውም።  በመሰረቱ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በህገ-መንግስቱ ውስጥ በዝርዝር መጻፍና ማንኛውም አገዛዝ እንዲከተለው መደረግ ያለበት መሰረተ ሃሳብ ነው። ስለሆነም መንግስትም ሆነ ኤክስፐርት ነን የሚሉ ከእንደዚህ ዐይነቱ ተግባር መቆጠብ አለባቸው። አገር ወዳድ ምሁሮችም ለአንድ አገር ዕድገት የሚመቸውን መንገድ የማሳየት ግዴታ አለባቸው።

ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚ ዕድገት ምን መምሰል አለበት!

እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ የታወጀው የተባበሩት መንግስታት የሚሌኒየም ዕድገት ዓላማ (MDGs) ከከሸፈ በኋላ እንደገና ይኸው ድርጅት 17 ነጥቦችን የያዘ ተከታታይነት ያለው ዕድገት (Sustainable Development) ተግባራዊ እንደሚያደርግ አውጇል። ከነዚህ 17 ነጥቦች ውስጥ እስከ 2030 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ የተባሉት መሰረታዊ ነገሮች፣ 1ኛ፟) ድህነትን እንዳለ ማስወገድ፣ 2ኛ) ረሃብን ማጥፋት፣ 3ኛ) ጥሩ የህክምና መስክ መዘርጋት፣ 4ኛ) ከፍተኛ የሆነ ትምህርት ማዳረስ፣ 5ኛ) ንጹህ ውሃና ጥሩ መጸዳጃ ማዳረስ፣ 6ኛ) እማራጭ የኃይል ስርጭት-ከነፋስ፣ ከወሃና ከጸሀይ የሚገኝ- ተግባራዊ ማድረግ፣ 7ኛ) ጥሩ የስራ መስክና የኢኮኖሚ ዕድገት መክፈትና ተግባራዊ ማድረግ፣ 8ኛ) ፈጠራና ጥሩ የመገናኛና የመመላለሻ መንገዶች ማመቻቸት፣ 9ኛ) በተቻለ መጠን በደሃና በሀብታም መሀከል ያለውን ልዩነት መቀነስ፣ 10ኛ) ጥሩና ተስማሚ የሆኑ የመኖሪያ ከተማዎችንና አካባቢዎችን መገንባትና፣ 11ኛ) ሰላምና እኩልነት የመሳሰሉት መስፈን ይገኙበታል። እነዚህን ወርቅ ዓላማዎች የጻፉት ሰዎች 1ኛ) ለምን የሚሌኒዩም 2015 ዓላማ ተግባራዊ እንደሆነ በፍጹም አልነገሩንም። 2ኛ) አሁን ባለንበት በግሎባል ካፒታሊዝም ዘመንና፣ እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ በአጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው የሚባሉት የጥቂት አገሮች ድርጅቶች በተለይም እንደኛ ያለውን አገርና መንግስት ለተከታታይ ዕድገት የማይስማማ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተል በሚያስገድዱበት ወቅት ከላይ የተጠቀሱት ዓላማዎች እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆኑ በፍጹም አልነገሩንም። ይህ ጉዳይ ግልጽ እስካልሆነ ድረስና፣ በተለይም ደግሞ የዓለም ኮሙኒቲው የሚመራበት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እስካልተወገደ ድረስ ተከታታይነት ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ልዩ ተቋማት፣ ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት የዕድገት ፕሮግራምና (UNDP) ሌሎችም የሚመሩበት ርዕዮተ-ዓለም ወይም የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳለ ተከታታይነት የሚኖረውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚቀናቀን ነው። በተለይም የመንፈስን የበላይነት ያስቀደመና ቁጠባን ተግባራዊ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አይደለም። ልቅ የሆነ የነፃ ንግድና ለሰው ልጅ የማያስፈልጉ ምርቶች መመረት በመሰረቱ አየርን የሚመርዙና ለተፈጥሮም ከባድ ጭነት ናቸው። እነዚህንና ከመሳሪያ ምርቶችና ከጦርነቶች ጋር የተያያዙ ነገሮችንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጉ የመጨቆጫ መሳሪዎች በዕቅዱ ውስጥ አልተካተቱም።

የላኛውን መሰረተ-ሃሳብ በመመርኮዝ አንዳንድ የታወቁ ግለሰቦች አገር ውስጥ የሚያድገው ኢኮኖሚ (Homegrown Economy) ተከታታይነት ካለው ዕድገት ጋር የሚስማማ ነው ብለው ቢያበስሩም፣ ምኑ ላይ ተከታታይነት እንዳለውና፣ እስከምን ድረስስ በተባበሩት መንግስታት ከተጻፈውና ከጸደቀው 17 ነጥቦች ጋር እንደሚስማማ በፍጹም አልነገሩንም። ለምሳሌ አገር ቤት ውስጥ ያድጋል ስለተባለው ኢኮኖሚ ድህነትንና ረሃብን ማስወገድ አለብን፣ ንጹህ ውሃን ማዳረስና የመጸዳጃ ሁኔታን ማስተካከል አለብን፣ እንዲሁም ሰው የሚኖርባቸውን ተስማሚ ከተማዎችንና አካባቢዎችን… ወዘተ. መገንባት አለብን ተብሎ በፍጹም አልተቀመጠም። የፖሊሲውን ይዘትና የገበያ ኢኮኖሚን እንደ ዓላማ ተግባራዊ ማድረግ ተከታታይነት ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በፍጹም የሚጓዝ አይደለም። የፖሊሲ አውጭዎቹ በተለይም ህዝባችን በአሳዛኛ ሁኔታ ውስጥ እንዴት እንደሚኖር በየቦታው እየተዘዋወሩ የከተማዎችን መቆሸሽና ውድቀት የተመለከቱ አይመስልም። እዚያው እየኖሩና በውስጡ እያለፉ የህዝባችንን አኗኗርና የቆሻሻ ቦታዎችን ሁኔታ እንደ ተፈጥሮአዊ አድርገው የሚመለከቱ ነው የሚመስለው። በአዲስ አበባ ብቻ በአለፉት 28 ዐመታት ቁጥራቸው የማይታወቅ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች (Slums) ተስፋፍተዋል።

ለማንኛውም በተለይም በአሁኑ ዘመን ተፈጥሮአዊ ሀብት በሚወድምበት፣ ወንዞች በሚቆሽሹበት፣ ከተማዎች ወደ ቆሻሻ መጣያነት በተለወጡበትና፣ የሰው ልጅ ንጹህ አየር ለመተንፈስ በተቸገረበት፣ በየከተማዎች ውስጥ የትራፊክ መጨናነቅ በበዛበት፣ ከፋብሪካዎች የሚወጣው ቆሻሻ ወንዞችንና አየሩን በሚበክልበት፣ በነፃ ንግድ ተሳቦ ለጤንነት የማይስማሙ ምግቦች በሚመረቱበትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ለበሽታ በተጋረጠበት፣ እንደ ሞንሳንቶ የመሳሰሉት የዓለምን ዘር የሚቆጣጠሩና ማዳበሪያና የተባይ ማጥፊዎችን እያመረቱ የእርሻ ማሳዎች…ወዘተ. እንዲበከሉ በሚያደርጉበት ዘመን ተከታታይነት ስላለው ዕድገት መታገል በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል። የአስተሳሰብ ለውጥ በሌለበትና መንግስታት ወደ አመጸኝነት በተለወጡበትና አማራጭ ሃሳቦችን አልሰማም፣ አልቀበልምም በሚሉበት ዘመን ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን ተግባራዊ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው።

ያም ሆነ ይህ ተከታታይነት የሚኖረው ዕድገት(Sustainable Economic Development) ተግባራዊ መሆን አለበት፣ አስፈላጊም ነው ብለን የምንነሳ ከሆነ ተከታታይነት ላለው ዕድገት እንቅፋት በሚሆኑ ነገሮች ላይ የግዴታ መነጋገር አለብን። ጤናማና ለተስተካከለ ዕድገት ማነቆዎች ናቸው ብለን በምናስባቸው ነገሮች ላይ በግልጽ እስካልተወያየን ድረስ የሚፈለገው ግብ በፍጹም ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ይህንን ጉዳይ ከተባበሩት መንግስታት ድህነትን መቅረፍና እኩልነትን ማስፈን አለብን እየተባለ በየአስር ዓመቱ የሚወጣውን ፕሮግራምና ውጤቱን የተመለከትነው ጉዳይ ነው።

ምናልባት በጥልቅ ተመራምረን እንደሆን በአገራችንም ሆነ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ለተስተካከለና ለጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት የሚሆኑት የመንግስታቱ መኪናዎችና አገዛዞች የሚመሩባቸው ፖሊሲዎች ናቸው። እንደሚታቀው በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በኢኮኖሚም ሆነ ሰፋ ባሉት የህብረተሰብ ጥያቄዎች ላይ ክርክርና ጥናት አይካሄድም። በአብዛኛዎች የገዢ መደቦች አስተሳሰብ ውስጥ አገርና ህዝብ ማለት ምን እንደሆኑና፣ ማንኛውም ሰው ህልምና ፍላጎት እንዳለው ግንዛቤ ውስጥ የተገቡ አይደለም። አብዛዎቹ የአፍሪካ መንግስታት በደመ-ነፍስ የሚመሩ የሚመስሉ ናቸው እንጂ፣ አንድ አገርና ህዝብ በስነ-ስርዓት መተዳደር እንዳለባቸውና፣ የጥሬ-ሀብቶችም አላቂ እንደሆኑ ግንዛቤ ውስጥ የተገቡ አይደሉም። ከዚህም ባሻገር የሚገነቡት ከተማዎችና የሚሰሩት ቤቶችና ህንፃዎች ከህዝብ ፍላጎት አንፃርና ከአካባቢ ሁኔታ እየተነፃፀሩ የሚሰሩ አይደሉም። ስለሆነም ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ሰፊውን ህዝብ የማድኸየትና ከተማዎችን የማቆሽሽና መኖሪያ ቦታዎች እንዳይሆኑ የማድረግ ባህርይ ያላቸው ውስጣቸው የተገነቡ(built-in) መሳሪያዎች አሉ። በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር ተከታታይነት ያለውና ለመጭው ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት ከፈልግን የግዴታ ከመንግስት የጭቆና መሳሪያና ከሚከተለው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅ አስፈላጊ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፥ ከውጭ የሚመጣብንን ግፊት አንቀበልም ብለን የመቃወም ልምድና ባህል እንዲኖረን ያስፈልጋል። አንድ መንግስት፣ ምሁራዊ ኃይልና ህዝብ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን አለባቸው። ይህ ጉዳይ የተፈጥሮ ህግ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ተከታታይነት ስላለውና የሰፊውን ህዝብ ችግር ሊፈታ ይችላል ብለን በምንገምተው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ መወያየት የምንችለው።

ከዚህ ስንነሳ 1ኛ) ተከታታይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት የመንፈስ ተሃድሶ በጣም አስፈላጊ ነው። 2ኛ) ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሁለ-ገብ መንፈስ ያለውና ብዙ ነገሮችን ያካተተ መሆን አለበት። 3ኛ) በተለይም መንግስትና ተቋማቱ ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከትርፍ አንፃር መተመን የለባቸውም። ዋናው ነገር ገቢዎች ዋጋን ብቻ የሚሸፍኑ መሆን አለባቸው። 4ኛ) መንግስትም ሆነ ግለሰብ ኢንቬስተሮች የህዝቡን ፍላጎት ሊያሟሉ በሚችሉና አካባቢን በማያቆሽሹ፣ በተጨማሪም እንደገና እንደ ጥሬ-ሀብት ሊያገለግሉ በሚችሉ (Renewable products) ምርቶች ላይ ብቻ መሰመራት አለባቸው። 5ኛ) በተቀሩት የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ምድር የሚገነቡት ከተማዎችና ቤቶች የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህጎች የሚጥሱ ናቸው። ሰፊውን ህዝብ የማግለልና ቆሻሻ ቦታዎች እንዲኖሩ የሚያደርጉ ናቸው። ለሽማግሌዎችና ለሚያድጉ ልጆች ተስማሚ አይደሉም። አብዛዋቹ ቤቶችና አካባቢው ጌቶዎች (Ghetto) ነው የሚመስሉት። ለአደጋ የተጋለጡና በተለይም ለሚያድጉ ህፃናት የሚስማሙ አይደሉም። በከተማዎች ውስጥም ሆነ በየአካባቢው በእግሩ የሚሄድ ሰው እንደልቡ ሊንቀሳቀስ በፍጹም አይችሉም። በመንገዶች ላይ መሽከርከር የማይገባቸውና አካባቢን የሚያቆሽሹ መኪናዎች ይነዳሉ። በዚህም የተነሳ በተለይም በአዲስ አበባና በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የመኪና አደጋ ይከሰታል፤ የብዙ ሰውም ህይወት ያልፋል። 6ኛ) በአገራችን ውስጥ መናፈሻና መጫወቻ ቦታዎችን የመገንባት ባህል የለንም። የዛፍ ማውደም ባህል በሰፊው ተስፋፍቷል። የብዙ መቶ ዐመታት ዕድሜ ያላቸው ዛፎች ካለ ጥናት ይቆረጣሉ። 7ኛ) ባለፉት 28 ዐመታት የአገራችን መሬት በኬሚካል ማዳበሪያና በተባይ ማጥፊያ ተመርዟል። ገበሬውም ከውጭ በሚመጡ ዘሮች ጥገኛ እንዲሆን ተደርጓል። 8ኛ) ከውጭ የሚመጡ ምግቦች የሰውን ጤንነት እያቃወሱ ነው። 9ኛ) በዕርዳታ ስም በአገራችን ምድር በየቦታው ተሰራጭተው የሚሰሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በቀላሉ ሊወገዱ የማይችሉ በሽታዎችና የማያስፈልጉ የወሲብ ግኑኝነትን አስፋፍተዋል። ይህ ዐይነቱ ተግባር ተከታታይነት ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚቃረን ነው። 9ኛ) በከተማዎችም ሆነ በየመንዶሮች አልፈው አልፈው የመጸዳጃ ቤቶች የሉም። አብዛኛው ሰው በየመንገዶች ላይ ነው የሚጸዳዳው። 8ኛ) አብዛኛው ህዝባችን ንጹህ ውሃን የማግኘትና የመጠጣት ዕድል የለውም። እንደዚህ እያልን ብዙ ነገሮችን መዘርዘር እንችላለን። ቁም ነገሩ ግን የጉዳዮችን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ቆራጥ እርምጃ መውሰዱ ላይ ነው። ሰው የሚኖራባት አገር የምንፈልግ ከሆነ የግዴታ እስካሁን ድረስ ካለን አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን። ክርክራችንና ጥናታችን ተከታታይነት በሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገትና የአገር ግንባታ ዙሪያ የሚሽከረከር መሆን አለበት። እነዚህም ፍልስፍናን፣ የተፈጥሮ ሳይንስን፣ የማሀበራዊ ሳይንስን ወይም ሶስዮሎጂን፣ የከተማ ዕቅድንና የቤት አሰራርን፣ ስለሚታደሱ የኃይል ማመንጫዎች (Renewable Energy) ጉዳይ፣ አካባቢን ስለመንከባከብ ጉዳይና፣ መናፈሻ ቦታዎችን ስለመስራት አስፈላጊነት፣ ስለማዕከለኛና ስለትናንሽ ኢንዱስትሪዎች…ወዘተ. መወያየትና መጻፍ አስፈላጊ ነው። እነዚህ ነገሮች የተከታታይ ዕድገት መሰረተ-ሃሳቦች መሆናቸውን በመገንዘብ በጭንቅላታችን ውስጥ መቋጠር አለን።  ከዚህ ውጭ የሚጻፍ ጹህፍ ወደ ንትርክና ወደ ግብግብ ነው የሚያመራን። አስተሳሰባችንና ዓላማችን ችግርን ፈቺ እንጂ ፈጣሪ መሆን የለበትም። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                                     fekadubekele@gmx.de

References:

Keen, Steve, Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned, New York, 2011

Keynes, John Maynard, The Theory of Employment, Interest and Money, London, 1967

Lawrence, Frederick, Byrne, Patrik, (eds), Collected Works of Bernard Lonergan:

Macroeconomic Dynamics: An Essay in Circulation Analysis, Toronto, 1999

Lietaer, Bernard, Ansperger, Christian, etl., Money and Sustainable Development, Vienna &

                               Berlin, 2013

Piketty, Thomas, Capital in the Twenty-First Century, London, 2014

Polanyi, Karl, The Great Transformation, New York, 1944

Raworth, Kate, Doughnut Economics: Seven Ways to Think Like a 21st-Century Economist,

               London, 2017

Reinert, Erik, How Rich Countries Got Rich… and Why Poor Countries Stay Poor, London,

                          2007

Rügener, Werner, The Capitalists of the Twenty-First Century, Koeln, 2018

Schulmeister, Stephan, The Way to Prosperity, Salzburg, 2018