Conscieousness and Non-Conscieousness
የነቃ የህብረተሰብ ክፍል ካለበት፣ ከሌለበት በምን ይለያል!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
መጋቢት 19፣ 2023
በመጀመሪያ ደረጃ የነቃ የሚለው ከንቃተ-ህሊና ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ሲሆን፣ የጭንቅላትን በከፍተኛ ደረጃ የመዳበር ጉዳይ የሚመለከት ነው። ንቃተ-ህሊና ያለው ሰው፣ ወይም ጭንቅላቱ በደንብ የዳበረ ሰው ካልዳበረው የሚለየው አንድን ነገር እያየ እንዳላየ ዝም ብሎ የሚያልፍ ሳይሆን ቆም ብሎ የሚያይና ሁኔታዎችንና ሂደታቸውን የሚመለከት ነው። ለምሳሌ በመንገድ ላይ ቆሻሻ ተከማችቶ ሲያይ፣ ወይም ደግሞ የተቸገሩ ሰዎች ከቆሻሻ ቦታ የሚበላ ነገር ሲፈልጉ፣ ወይም ደግሞ በአንድ አካባቢ ሰዎች በተዝረከረከና አካባቢው በገማ ቦታ ሲኖሩ ዝም ብሎ የሚያልፍ ሳይሆን ፎቶ በማንሳት ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ? ወይም ደግሞ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጥያቄ ለማንሳትና ለመመርመር ይገደዳል። አልፎም የሁኔታውን አሳሳቢነት ከተረዳ በኋላ ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላ በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍልና በአገዛዙ ዘንድ ግንዛቤ(Awareness) እንዲኖር ሰፋ ያለ ሀተታ በመስጠት የሚመለከተው መስሪያ ቤት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ለማድረግ ይጎተጉታል።፡
ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ንቃተ-ህሊናው የዳበረ ሰው በዚህ ሳይወሰን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚታዩ ስነ.-ምግባርና ግብረ-ገበነት የጎደላቸው ነገሮች በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል፣ በራሱም የመንግስት አካል ነኝ በሚለው ሲፈጸም ይህ ዐይነቱ ድርጊት እንደተራ ነገር እንዳይወሰድ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖር ሳይታክት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለማስተማር ይሞክራል። ለምሳሌ ወጣቱና ደሃው የህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በፖሊስ ሲመናጨቁ ወይም ሲደበደቡ ሲያይ ዝም ብሎ አያልፍም። ቆም ብሎ በማየት የተወሰኑ ሰዎች እንዲያግዙት በማድረግ ፎትግራፍ ካነሳ በኋላ ፖሊሶች ለምን ወጣቶችን እንደሚደበድቧቸውና በህግም ተፈቅዶ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። ከዚህም በማለፍ መታወቂያቸውን በመጠየቅና በመመዝገብ ለሚመለከተው መስሪያቤት ክስ ያቀርባል። ይህ ዐይነት አካሄድ ሊሰራ የሚችለው በእርግጥም የሰለጠነ መንግስትና ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ፍርድቤት ሲኖር ብቻ ነው።
ንቃተ-ህሊናው የዳበረ የህብረተሰብ ክፍል ባለበት አገር ውስጥ መንግስትን ወይም አንድን አገዛዝ ተገን በማድረግ በህዝብ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዐይነት በደል እንዲቆም ማድረግና የህግ የበላይነት እንዲከበር ውትወታ ማድረግ በተለይም የነቃው የህብረተሰብ ክፍል ተግባር መሆን አለበት። ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቤታቸው ካለአግባብና ቀደም ብሎ መተኪያ መኖሪያ ቤት ሳይሰጣቸው በላያቸው ላይ ዝም ብሎ የሚፈርስ ከሆነ ጉዳዩ በአስቸኳይ እንዲቆም በመተጋገዝ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ለመወሰድ ይሞክራል። ፖሊሶችም በኃይል የሚመጡ ከሆነ ሁኔታውን በኃይል ለመመለስ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለበት። ምክንያቱም ለፖሊስም ሆነ ለሌላ የመንግስት አካል ህዝብን አጎሳቅል፣ ቤቱን በላዩ ላይ አፍርስበት የሚል ከእግዚአብሄር የተሰጣቸውው ልዩ መብት ስለሌላቸው የመንገስት አካል ነኝ የሚለው ያነገተውን ጠበንጃ ተማምኖ በደመ-ነፍስ በመመራት በህዝብ ላይ በደል የሚፈጽም ከሆነ ይህ ዐይነቱ ድርጊት በተባበረ ክንድ ተገቢውን መልስ ማግኘት አለበት።
በአቢይ አህመድና በግብረ-አበሮቹ የሚመራውን ያለፈውን አምስት ዓመት የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት በዚህች አጭር ዓመታት ውስጥ ህዝባችን፣ በተለይም ደግሞ አማራውና ክርስቲያኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ አፀያፊ ነገሮች በመቆጠር መደረግ የሌለባቸው ወንጀሎች በሙሉ ተፈጽመውባቸዋል። በወያኔ ዘመን የደረሰባቸው ግፍ አላንስ ብሎ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከተፈጠረችበት ዘመን ጀምሮ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈጸሙ ስህተቶች ወይም ወንጀሎች በሙሉ በጅምላ አማራው የፈጸማቸው አድርጎ በመቁጠር ስልጣንን የያዘው አቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ በሙሉ በዝቅተኛ ስሜት በመመራትና፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረ-አበሮቹ በመደገፍ በአማራውና በክርስቲያኑ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ላይ አንድ ሰው በሌላው ላይ ማድረግ የማይገባውን አሰቃቂ ድርጊቶች ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ይገኛሉ። አማራውና የክርስቲያኑ የህብረተሰብ ክፍል የመሰረቷቸው መንደሮችና ከተማዎች ከእነ መደብሮቻቸውና ቤቶቻቸው ጋር እንዳለ ወድመዋል። ቁጥሩ የማይታወቅ ህዝብ በተለይም በወለጋ ውስጥ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን በመታረድ የአንዳንዱ ብልት ደግሞ ኦነግ ሸኔ በሚባል በመንግስት በሚደገፍ ጭራቅ ቡድን እየተቆረጠ ይበላል። አማራን ከአካባቢው ማጽዳት ያስፈልጋል በሚል ሰበብ፣ ሽማጋሌዎች፣ ወጣት ገበሬዎችና ሌሎችም በአቢይ አህመድና በሺመልስ አብዲሳ የሚጠመዘዘው ኦነግ ሽኔ በሚባለው ጭራቅ ቡድን እንደከብት ይታረዳሉ። በተለይም ተጋብተው የሚኖሩ አማራዎችና ኦሮምዎች ጋብቻቸው እንደወንጀል በመቆጠር ሁለቱም ይጉላላሉ። እንደምንሰማውና እንደምንከታተለው ከሆነ አንድ ያረገዘች ሴት ለወሊድ ወደሆስፒታል በምትሄድበት ጊዜ ከማን እንዳረገዘች ተጠይቃ በደህና ከተገላገለች በኋላ ልጇን ተነጥቃ እንድትባረር ትደረጋለች። ባልየውም እየተሳደደ ጥርሱ እስኪወልቅ ድረስ ይደበደባል። ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ተራው የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ ሳይሆን፣ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አምስት ወይም ስድስት ዓመት ያህል የህክምና ትምህር ከተማሩ በኋላ ብዙም ልምድ ሳይኖራቸው ሀኪሞ ቤቶች ተቀጥረው በሚሰሩ ሀኪሞች ነው። በመሰረቱ ማንኛውም ሀኪም ከህክምና ሙያው በተጨማሪ ስነ-ምግባር መማር አለበት። ይህም ማለት ትምህርቱን ጨርሶ በሚቀጠርበት ጊዜ አንድ ታማሚ ሰው ለህክምና እሱ ጋ ወይም ሆስፒታል ሲሄድ ዘርህ ምንድነው? ብሎ የመጠየቅ መብት የለውም። ከየትኛውም ብሄረሰብ ይምጣ ማንኛውም ግለሰብ የህክምና ዕርዳታ ሲያስፈልገው ማንኛውም ሀኪም የህክምና ዕርዳታ የማድረግ ግዴታ አለበት። ሊጠይቅ የሚችለው ታማሚው ለምን እንደመጣና፣ የት የት ቦታ ላይ እንደሚያመውና፣ ከመቼስ ጊዜ ጀምሮ እንደሚያመው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ስፖርት ይሰራ ወይም አይሰራ እንደሆን፣ በበቂው እንቅልፍ ይተኛ ወይም አይተኛ እንደሆን፤ አልክሆል ይጠጣ ወይም አይጠጣ እንደሆን፣ ሲጋራም ያጨስ ወይም አያጨስ እንደሆን፣ አ፣እጋገቡስ እንዴት እንደሆነ ብቻ ነው የመጠየቅ መብት ያለው። እነዚህን ነገሮች መጠየቁ በተቀራራቢ የበሽታውን ምክንያት መነሻ ለመገንዘብ ሊረዳው ይችላል። ከዚህ ውጭ ዘሩ ምን እንደሆነና፣ ከየትኛው ብሄረሰብ ከመጣች/ከመጣ ሴት ወይም ወንድ ጋር እንደምትኖር ወይም እንደሚኖር የመጠየቅ መብት የለውም። እንደዚህ የሚያደርግ ሀኪምና በሽተኛውን የሚያመናጭቅ፣ ወይም አንድ ሴት በደህና የተገላገለችውን ህጻን ነጥቆ የሚያባርር ሀኪም እዚህ በሰለጠነው የካፒታሊስት ሀገር ቢሆን ኖሮ በህግ ያስጠይቀዋል። ነገሩም ተጣርቶ በደንብ ከተረጋገጠ የህክምና ፈቃዱ በመነጠቅ ለብዙ ዓመታት በሙያው እንዳይሰራ ይታገዳል። በሀገራችን ውስጥ በታማሚውም ሆነ በሌላው ህዝብ ላይ መንግስትን ተገን በማድረግና ማንም ሊጠይቀን አይችልም በማለት የሚፈጸመው ወንጀል ለመሆኑ ያቺ ኢትዮጵያ ሰው የበቀለባት አገር ነች ወይ? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። ለመሆኑ በምን ምክንያት ነው በተለይም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል አመጸኛና አረመኔ ለመሆን የበቃው? ጭንቅላትን የሚያዞር፣ እንደሰው እንዳያስብ የሚያደርገው የሚወስደው ድረግ አለ ወይ? ሌሎች የመንግስት አካላትስ እንደዚህ ዐይነቱን በህዝብ ላይ የሚፈጸም ቅጥ ያጣ በደል ሲሰሙ ምን ይሰማቸዋል? የህዝብ ተጠሪዎችስ ነን የሚሉ እነዚህን ነገሮች በማንሳት በፓርሊያሜንት ውስጥ ይከራከራሉ ወይ? ይህ ዐይነቱ አስከፊ ተግባርስ እንዲቆም የሚጸድቁ ህጎችስ አሉ ወይ?
እነዚህና ሌሎች እጅግ ለጆሮ የሚዘገንኑ ነገሮች በተለይም በአለፉት አምስት ዓመታት በአገራችን ምድር እየተለመዱ በመምጣት የመንግስት አካላት ነን የሚባሉት በተራው ህዝባችን ላይ ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸሙ ነው። የሚጠይቃቸውና ለመብቱም የሚታገል ሰው ወይም ድርጅት፣ ወይም ደግሞ የነቃ የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ በአገሪቱ ምድር ውስጥ የመንግስት አካላት ነን ከሚሉት በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ውስጥ ጋጠ-ወጥ ድርጊቶች ይፈጸማሉ። አንዳንዶች ውሃና መብራት ለብዙ ወራት አላገኘንም ብለው ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ በጥይት ይቆላሉ። በአገራቸው ምደ ባይተዋር በመሆን መንፈሰ-አልባ በሆኑ ደንቆሮዎች ይሰቃያሉ። ተማርን የሚለውና አንዳንዱም የፖለቲካ ድርጅት አለኝ የሚለው ነገሩን እንዳለየ በማየት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ላለመታማት በሚል መንግስት አካሄዱን ማስተካከል አለበት፣ ዝም ብሎ ማየት የለበትም የሚል ማሳሰቢያ ነገር ይሰጣል። መንግስት የሚባል በሌለበት፣ ወይም ደግሞ ራሱ መንግስት የሚባለው በውንብድና ስራ በተሰማራበትና ህዝብን በሚያሰቃይበት አገር መንግስት እንደዚህ ቢያደርግ ይሻላል እያሉ ማላዘን አላዋቂነትን ነው የሚያረጋግጠው።
አቢይና ግብረአበሮች ስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ የኢትዮጵያን ስዕል እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ለመቀየርና ለአረብ ቱጃሮች ለመቸብቸብ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በአገራችን ምድር የማይፈጽሙት ወንጀል የለም። ገንዘብ ከየት መጣ ሳይባልና ፓርሊያሜንት ውስጥ ወይም በሚመለከተው መስሪያ ቤት ሳይጣራ ካለ ዕቅድ ባለአምስትና በላሰባት ኮከብ የናጠጡ ሆቴል ቤቶች ይሰራሉ። ሆቴል ቤቶችም ውስጥ ለማደር ለአንድ ምሽት ብቻ አምስት ሺህ ዶላር ያስከፍላል። ከዚህም በተጨማሪ ሞልስ በመባል የሚታወቁ አዳራሾችና ፓርኮች ይሰራሉ። በተቀራኒው ደግሞ ህዝባችን መኖሪያ ቤት አጥቶ በየቆሻሻ ቦታዎች እንዲኖር ተገዷል፤ በኑሮ ውድነትም የሚንገፈገፈው ህዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ እወክለዋለሁ የሚለው የአቢይ አህመድ አገዛዝ ህዝባችንን በመናቅ በደንቆርው የሱዳን መሪ በሚገዛና በሚታዘዙ የሱዳን ወታደሮች በአማራው ክልል ውስጥ እስከ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ በመዝለቅና መሬቱን በመቆጣጠር በህዝባችንም ላይ ግድያን ይፈጽማሉ። የክልሉ አስተዳዳሪ የሆነው አማራ ነኝ የሚለውና ወታደሩም ሆነ ልዩ አካላት ይህንን የአቢይ አህመድን ወንጀለኛና ታሪከ-ቢስ ድርጊት እንደ ትክክል አድርገው በመቁጠር በህዝባችንና በአገራችን ላይ የወንጀሉ ተባባሪ በመሆን ብሄራዊ ነፃነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲገፈፍ ለማድረግ በቅተዋል።
ለማንኛውም እንደዚህ ዐይነቱ በአቢይ አህመድና በግብረአበሮች በማንአለኝበት በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚፈጸመው ባህለ-አልባ ድርጊት በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው በሚጠሩት ውስጥ ተፈጽሞ አያውቅም፤ ሲፈጸምም አይታይም። ቻይናና ራሺያ እንዲህም ሰሜን ኮሪያ የማንም የውጭ ኃይል ተገዢ መሆን የለብንም ብለው ኢኮኖሚያቸውን ሲገነቡና ኃይላቸውንም ሲያጠናክሩ በአቢይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ተብዬው አገራችንና ህዝባችንን ለማዋረድ የማይፈጽመው ወንጀል የለም። ስንትና ስንት ወንጀል ከሰራው የወያኔ የወንበዴ መሪዎች ጋር ሆኖ በመደራደር ስም አገራችንን ለመቀራመትና በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎቹ እንድትበዘበዝ ለማድረግ የማይሸርበው ተንኮል የለም። አንድ ሰሞን ከኤርትራው ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የጦፈ ፍቅረኛነት ከመሰረተና ሽር ጉድ ካለ በኋላ አሁን ደግሞ ኤርትራን እንደዋና ጠላት በማየት ለጦርነት በመዘጋጀት ላይ እንዳለ እየሰማን ነው። አቢይ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እየተጠመዘዘና እየታዘዘ አገራችንና ህዝባችንን የማይወጡት ማጥ ውስጥ እየከተታቸው ነው። ለመሆኑ እንደዚህ ዐይነቱ ፖለቲካስ ምን ዐይነት ፖለቲካ ይባላል? በመሰረቱ እንደአቢይ አህመድ የመሳሰሉትም ሆነ በተለይም የኦሮሚይና የአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ነን የሚሉት በምንም ዐይነት ስልጣን ላይ የመውጣት መብትና ችሎታም የላቸውም ነበር። ለምሳሌ ስለቻይና የሚወጡትን ተከታታይ ዘገባዎችና ሰሚናሮች ለተመለከተ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ ክሚገኙት አገዛዞች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ብቃትነ ያለውና(The most competent government in the world) ከካፒሊስት አገሮችም ጋር ሲወዳደር ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ ነው። ለከፍተኛ ስልጣን የሚታጩት በሙሉ በመጀመሪያ ደረጃ በትናንሽ መንደሮችና ከተማዎች ብቃትነታቸውንና በጥሩ የማስተዳደርና አካባቢውን በመገንባት ያስመሰከሩ መሆን አለባችው። ከዚህ በተጨማሪ በየጊዜው ይገመገማሉ። ባጭሩ ስንትና ስንት ፈተናዎችን ካለፉ በኋላ ነው ለከፍተኛ ስልጣን የሚታጩት። ለዚህም ነው ቻይና በአርባ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትላልቅ ከተማዎችን ብቃትነት ባለው መንገድ መገንባቷ ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ባለቤትም ለመሆን የበቃችው። በማግኔት ሃዲድ ላይ የሚነዱ ፍጥነታቸው በሰዓት ከአራት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ ባቡር በቻይና ምድር በብዙ አካባቢዎች ተግባራዊ ለመሆን በቅቷል። ከድሮው የትላልቅ ፎቅ ቤት መስራት ስህተታቸው በመማር ቤቶች ዝቅ ተብለው በመሰራት ከተማዎችና አካባቢዎቻቸው በዛፎች እንዲሞሉ እያደረጉ ነው። ቻይና ከሌሎች የካፒታሊስት አገሮች ጋር ስትነፃፀር አካባቢን ሊያስጠብቁ የሚችሉና ከአካባቢው ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመስራት ተቀዳሚ ቦታን ይዛ ትገኛለች። በከተማዎች ውስጥም የሚሽከረከር መኪናዎችም በተቻለ መጠን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚነዱ መሆን እንዲችሉ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ምርምር በመደረግ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። ከዚህም በላይ ኢኮኖሚውና ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለሰፊው ህዝብ አስፈላጊውን ግላግሎቶች የምትሰጥ አገር ለመሆን በቅታለች። በተጨምሪም በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ወንጀልን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘዴ በመፍጠርና በመመዝገብ ህዝቧን ለመቆጣጠር ችላለች።
የቻይናን በአንድ ወጥ አገዛዝ መመራት አስመልክቶ በየጊዜው ጥናቶችና ክርክሮች ይካሄዳሉ። ቻይና የግዴታ የካፒታሊስት አገሮችን ምሳሌ በመከተል ለብዙሃን ፓርቲዎች የፖለቲካ መድረኩን ክፍት ማድረግ አለባት እየተባለ ውትወታ ይደረጋል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በቻይና ምድር ውስጥ ሊሰራ እንደማይችልና፣ የቻይና ህዝብ በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር መተዳደሩ ይህን ያህልም አልተጎዳም ብለው የሚከራከሩ፣ የቻይናም ሆነ የካፒታሊስት አገሮች ምሁራን አሉ። ታዲያ የቻይናን የዕድገት ሂደት ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠው ቻይናዊና አንድ እንግሊዛዊ ምሁሮች እንዳረጋገጡት የቻይና መንግስት በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ መንግስታ በብቃትነት ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝ በአማስረጃ በምደገፍ ተናግረዋል። በተነጻጻሪም እንደ ጆርጅ ቡሽና ቀደም ብሎ ጃፓንን ያስተዳድሩ የነበሩ ጠቅላይ ሚኒሰተሮች ቻይና ውስጥ ቢሆኑ ኑሮ ላይ ድረስ የመውጣት ዕድል ሊኖራቸው አይችልም በማለት በመሀከላቸው ያለውን የአስተዳደርና የብቃትነት ልዩነት ለማስረዳት ሞክረዋል። ነገሩ ቀላል ነው። እነ ጆርጅ ቡሽ የመሳሰሉት መሪዎች ቀድሞውኑ በተዘጋጀና በተገነባ የካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ስለተወለዱና ስላደጉ ካፒታሊዝምን እንደገና መፍጠርን አገርን መገንባት አያስፈልጋቸውም። የቻይና መሪዎች ግን ሀ ብለው በመጀመር ነው ወደ ተወሳሰበና ብቃትነትም ወዳለው ስርዓት ውስጥ ለመምጣት የቻሉት። በዚህ ዐይነቱ የተቀላጠፈና ለህዝብ ተገዢነት ፖለቲካቸው 80% የሚሆነውን የቻይናን ህዝብ በሰላሳ ዓመት ዕድሜ ውስጥ ከድህነት በማላቀቅ የተሻለ ኑሮ እንዲያገኙ አስችለዋቸዋል። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን የወያኔም ሆነ አሁን ስልጣን ላይ ያለው በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ ቻይና ውስጥ ቢሆኑ ኖሮ ከዘበኘነት ሊያልፉ የሚችሉ አልነበሩም። የታሪክ አጋጣሚና የአገራችንም ዕጣ ፈንታ በመሆን ህዝባችንና አገራችን በእንደነዚህ ዐይነት ከሂደዎች፣ አገርንና ህዝብን በታታች በሆኑና፣ ምንም ዐይነት ብቃት ሳይኖራቸው ስልጣን ላይ ቁጥጥ ባሉ ወንበዴ ኃይሎች እንዲገዙ ተገደዋል።
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ የተገደድኩት ሰሞኑን ከፍርድቤትና የህግ የጥገና ለውጥ ጋር ተያይዞ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር በቤንጃሚን በኔታንያሁ የሚመራው አገዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ የፈለገውንና የረቀቀውን ህግ አስመልክቶ የሚደረግ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚሳተፍበት ሰላማዊ ሰልፍንና ዜናዎችን በመከታተሌ ነው። በአዲሱ የፍርድቤትና የህግ የጥገና ለውጥ መሰረት የመንግስት ባለስልጣናት፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆንበትንና ከፍተኛው የፍርድቤት አካል የሆነውን መብት የሚገፍና፣ አብዛኛው ህግ በቀላል ድምጽ ሊያልፍና ሊተገበር የሚችልበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው። ይህንን የተከታተለው የነቃው የእስራኤል የህብረተሰብ ክፍል፣ በአገልግሎት ላይ ያሉም ሆነ ተጠባባቂ ወታደሮችም ሆነ ዳኞች፣ እንዲሁም ጠበቆች ሁሉ ሳይቀሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት የፍርድቤቶች መብት በምንም ዐይነት መቀረፍ የለበትም፣ የህግም የበላይነት መከበር አለበት በማለት በከፍተኛ ተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። እንደሚታወቀው ኔታንያሁና ከእሱ ጋር አዲስ አገዛዝን የመሰረቱት ፓርቲዎች (Right Wing Radical Groups) በፖለቲካ አመለካከታቸው አክራሪና ሁሉንም ነገር በጉልበት ለመፈጸም የሚጣጣሩ ናቸው። ፖለቲካ የሚባለውን አንድን ህብረተሰብ በጥበብና በስርዓት የማስተዳደሪያ መሳሪያ ወደ እነሱ አመለካከት በመለወጥ የኋሊት ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙ ኋላ ቀር የሆኑ ኃይሎች ናቸው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ለጊዜው እነ ኔታንያሁን የሚጠቅም ቢመስልም የእስራኤልን ህዝብ የሚጎዳና እንደ አገር የመቀጥልም ሁኔታዋን በጥያቄ ውስጥ የሚያስቀምጥ ነው። ኔታንያሁንና አገዛዙ ከዚህ አልፈው በመሄድ በፊልም ላይ፣ በቲአትርና በሜዲያው ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ለየት ያለ አመለካከት ያላቸውና የስለጠኑ እስራኤላውያን ሁኔታ ስላንገፈገፋቸው አገራቸውን ጥለው በመውጣት ላይ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ እነ ኔታንያሁን በፓሌስቲኒያን ህዝብ ላይ ያላቸውን አደገኛ አመለካከት በማጤን ሁለቱም ህዝቦች በሰላም ሊኖሩ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚሉ ምሁራን በአጠቃላይ ከሃዲዎች በመባል ይወነጀላሉ። በአሁኑ ወቅት እስራኤል ከውስጥ አልፎ አልፎ ከፓሊስቲናውያን ጋር በግጭት ውስጥ ስትገኝ፣ ከውጭ ደግሞ በሊባኖኑ ሂስቦላና በኢራንና በሶሪያ የተከበበች አገር ለመሆን በቅታለች። በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም በመደገፍና ቴክኖሎጂዎችን በማግኘት በአካባቢው እኔው ብቸኛው ኃያል መንግስት ነኝ በማለት ይቀናቀኑኛል ክምትላቸው አገሮች ጋር ሁሉ በመጣላትና አልፎ አልፎም ድንበሯን በማለፍ ሌሎች አገሮችን በአውሮፕላን በመድብደብ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ የእስራኤልን ህዝብ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እየከተቱት ነው። አሁን በቅርቡ በሳውዲ አረቢያና በኢራን መሀከል በቻይናዎች አደራዳሪነት የተደረገው የመቀራረብ ስምምነት ለእስራኤል የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካዋ የሚያመች አይደለም። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንደዚህ ዐይነት የውስጥ ግጭት እንዲፈጠር አላስፈላጊ ህግ ማውጣት አደገኛ መሆኑን የተመለከቱትና፣ የፖለቲከኞችን ጡንቻ የሚያፈረጥምና የህግ የበላይነትን የሚያዳፍን መሆኑን የተረዳው የነቃው የእስራኤል የህብረተሰብ ክፍል ወደ ውጭ በመውጣትና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ አገዛዙን መውጫና መግቢያ አሳጥቶታል።
ይህን ትተን ወደ ፈረንሳይ ስንመጣ ደግሞ የማክሮን አገዛዝ ከፓርሊያሜንቱ፣ ከወዝ-አደሩ የሙያ ማህበርና፣ በጠቅላላው የሲቪል ማህበራት ጋር ሳይወያይና ሳይደራደር የጡረታን ጊዜ አስመልክቶ የፕሬዚደንቱን የማጽደቅ ኃይል የሚያወሳውን አንቀጽ በመመርኮዝ በራሱ ኃይል ብቻ በመተማመን ወደ ተግባር መመንዘር አለበት ያለው ህግ በነቃው የፈረንሳይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን አላስገኘለትም። ስሞኑን እንደምንከታተለው ከሆነ በፖሪሲም ሆነ በተለያዩ ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ አገዛዙን መውጫና መግቢያ ያሳጣው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የሚሳተፍባቸው ሰላማዊ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ አላት የምትባለው አገራችን ጋር ስንመጣ ግን ሁኔታው ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው። ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የተማረና የነቃ የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ ህዝባችን በጥቂት ጋጠ-ወጦች ፍዳውን እንዲያድ ተፈርዶበታል። ላዩ ላይ ቤቱ ይፈርስበታል፤ መንገድም ላይ እንዲወድቅ ይደረጋል። አቅመ-ቢስ ከመሆኑም የተነሳ አንዳንዱ ራሱን ይገዳልል። በአቢይ አህመድና በግብረአበሮቹ፣ በአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ድጋፍና ተባባሪነት በህዝባችን ላይ እስካሁን ድረስ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶችና የታሪክ ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ወታደሩ እንዳለ በአቢይ ቁጥጥር ስር በመደረጉ በተለይም በሰሜኑ ክፍል በወያኔ አማካይነት በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን የግድያና የዝርፊ ጥቃት ብቃትነት ባለው መልክ በመከላከል ወያኔን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ እርምጃ በመውሰድ ከዚያች ምድር እንዲጠፋ ለማድረግ ተስኖታል። የኢትዮጵያ ወታደር ተብዬው በማጥቃት ላይ በሚገኝበት ጊዜ አፈግፍግ ይባላል። በዚያውም መጠንም የወያኔ ወንበዴዎች እየመጡ ህዝብን ይገድላሉ፤ መንደሮችን በማፈራረስ ሀብትንም ይዘርፋል። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው ወታደሩ ባልተማሩና፣ ቢማሩም እንኳ ምሁራዊ ብቃትነት በሌላቸው ኃይሎች እንደተያዘ ነው። የሰለጠነና በሁሉም አቅጣጫ የሚያስብ ወታደራዊ ኃይል ቢኖር ኑሮ እነ አቢይንና ግብረአበሮቹን በቀላሉ ከስልጣን ላይ በማንሳት ተገቢውን ቅጣት መስጠት በተቻለ ነበር። አገር ሲፈራርስና ህዝባችን ፍዳውን ሲያይ፣ ሲፈናቀልና ሲገደል ዝም ብሎ የሚያይ ወታደርና ሌላ የፀጥታ ኃይል እንደወታደር ሊቆጠር አይችልም። በአንዳንድ የወታደሩ መኮንኖች የሚወራው አባባል፣ “ወደድንም ጠላንም አቢይ ጠቅላይ ሚኒስተራችን ነው፣ እሱ ያዘዘንን መቀበል አለብን” የሚለው አካሄድ በፍጹም ሊሰራ አይችልም። ህዝብን የሚጎዳና አገርን የሚያፈራርስ አገዛዝ ዝም ብሎ መታየት የለበትም። አንድ ጠቅላይ ሚኒስተርም የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል የሚል ከእግዚአብሄር የተሰጠ ህግ የለም። ያለነው በ21ኛ ክፍለ-ዘመን ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስተሩና ሌሎችም የአገዛዙ አካሎች የህግን የበላይነት በመጣስ የፈለጋቸውን የማድረግ መብት የላቸውም።
ለማንኛውም የነቃና የተደራጀ የህብረተሰብ ክፍል ቢኖር ኖሮ እንደነዚህ ዐይነት ኃይሎች አንድም ቀን ስልጣን ላይ የመቆየት መብት ሊኖራቸው ባልተገባ ነበር። በህዝባችንም ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃት ባልደረሰ ነበር። ያለነው በሚያሳዝንና በሚያሳፍርም የታሪክ ወቅት ውስጥ ነው። የነቃው የአውሮፓው የህብረተሰብ ክፍልና፣ የቻይናና የራሺያ አገዛዞች አገራችንና ህዝባችን በመንፈሰ-አልባ ኃይሎች መመራቷን ሲመለከቱ እየሳቁብንም፤ እያዘኑልንም ነው። ታዲያ ይህንን ዐይነቱን አገርን አፍራሽና ህዝብን በታታኝ ድርጊት እስከመቼ ድረስ ነው የምንመለከተው? ራሳችንን እየመላለስን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። አሜሪካንና አውሮፓውያኖች ያድኑናል ብለን የምንጥብቅ ከሆን ምንም ነገር አልገባንም ማለት ነው። አገራችንና ህዝባችንን ማዳን የምንችለው በራሳችን ኃይልና ዕውቀት ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ ዐይነቱ የተቀደሰ ተግባር በአዲስ መንፈስ መዘጋጀት አለብን። ጊዜው የመሸ ቢመስልም፣ የማይቻል ነገር ስለሌለ የሸዋጅና የአረጁ ኃይሎችን ሰበካ ሳይሰሙ ለሁለንተ-ገብ ትግል መዘጋጀት የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ግብግብ ለሌባ ያመቻል እንደሚሉት አነጋገር፣ የአሁኑን የአገራችንን አስቸጋሪ ሁኔታ የተገነዘቡና ቀደም ብለው ስንትና ስንት ወንጀል የሰሩ ኃይሎች በአገራችን ምድር ላይ አንድ ነገር ቢፈጠር በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዚም በመደገፍ ስልጣን ላይ ለመውጣት ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛሉ። አገራችን በምንም ዐይነት በከሃዲዎችና ለውጭ ኃይሎች በአደሩ እጅ ስር መውደቅ የለባትም። እነዚህ ዐይነት ያረጁና ምንም ዐይነት የፖለቲካ ብቃትነትና ፍልስፍና የሌላቸው ኃይሎች ዝም ብለው ቢቀመጡ ትልቅ አስተዋፅዖ አደረጉ ማለት ነው። መልካም ግንዛቤ!!