The Fate of a given country and its people will be decided by 2-5% of the people
የአንድ አገርና ህዝብ ዕድል ሊወሰን የሚችለው ከ2-5% በሚሆነው
የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው !!
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ታህሳስ 14፣ 2023
በአሁኑ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ግሎባላይዜሽን እየተባለ በሚጠራበትና፣ የሰውም ልጅ ዕድል በሳይንስና በቴክኖሎጂ በሚገለጽበት ዘመን በተለይም በአፍሪካና በማዕከለኛው፣ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የህዝቦቻቸው አለኝታ ከመሆን ይልቅ ይበልጥ ጨቋኝ እየሆኑና፣ ህዝቦቻቸውም ጭቆናንና ድህነትን ለመቋቋም ባለመቻላቸው የቻሉት አገራቸውን እየጣሉ ወደ ካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም ወደ ታላቁ አሜሪካና፣ እንዲሁም ወደ ጀርመን፣ እንግሊዝና ጣሊያን እንዲሰደዱ እየተገደዱ ነው። በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሰፈኑት አገዛዞች የግዴታ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የብዝበዛ፣ የጭቆናና፣ የማደኸያና የማደንቆሪያ ሰንሰለት ውስጥ የተካተቱና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አገርንና ባህልን የማፍረስ ዕቅድ አስፈጻሚዎች በመሆናቸው በእነዚህ አህጉራት ውስጥ የተትረፈረፉ የጥሬ-ሀብቶች ቢኖሩም የጥሬ-ሀብቶቹ በቀጥታ በአሜሪካን፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳና በፈረንሳይ የጥሬ-ሀብት አውጭ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር በመሆናቸውና፣ ጥሬ-ሀብቶችም ሳይፈበረኩ በቀጥታ ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ ስለሚጓዙ የየአገሩ ህዝቦች በምንም ዐይነት ተጠቃሚ ሊሆኑ በፍጹም አልቻሉም። ሰፊው ህዝብ መጻፍና ማንበብ፣ እንዲሁም የየፓርቲዎችን ፕሮግራሞች አንብቦ ትርጉማቸውን ለመረዳት በማይችልበትና የፖለቲካ ትርጉምን በማይገነዘብበት ሁኔታ ውስጥ በምርጫ ስም ስልጣን ላይ የሚወጡ መሪዎች በነፃ የገበያ ኢኮኖሚና በሊበራላይዜሽን ስም ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ድህነትን ከማስወገድና ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅም የተሰተካከለ ኢኮኖሚ ከመገንባት ይልቅ ለምን ኋላ-ቀርነት እንዲፈረጥምና አገዛዞችም የባሰ ጨቋኝና ዘራፊ እንደሚሆኑ ለመጠየቅ የሚችል የለም። አንዳንድ የሚጠይቁ ቢኖሩም ተሰሚነት ስለማይኖራቸው ወይም ደግሞ ይህ አስተሳሰብ የኮሙኒስቶች ነው በመባል እንዲሸማቀቁ ስለሚደረጉ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብርና ሰፊው ህዝብም የማወቅና የማገናዘብ ዕድል እንዳያገኝ ለመደረግ በቅቷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአራት ዓመቱ በተለይም በደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ የሚደረገው ምርጫ ያለውን ሁኔታ ከማባባስና ጭቆናን ከማጠናከር በስተቀር የየህዝቦችን የኑሮ ሁነታ ሲያሻሽልና የመኖር ተስፋቸውንም ብርሃን ሲያንፀባርቅበት በፍጹም አይታይም። ሰሞኑን ዜናዎችን ተከታትለን እንደሆን በ23.10.2023 ዓ.ም አርጀንቲና ምርጫ ተካሂዶ የመጨረሻ መጨረሻ በሁለት ተጣርተው በቀረቡ ተወዳዳሪዎች መሀከል በተካሄደው የፕሬዚደንት ምርጫ በአሸናፊነት የወጣው በጣም ቀኝ የሆነና ራሱን የካፒታሊስት አናርኪስት ነኝ ብሎ የሚጠራውና፣ ከቀኝ በስተቀር ሌሎች የግራ መሰል ወይም ማህበራዊ አስተሳሰብ አላቸው የሚላቸውን በሙሉ አጠፋቸዋለሁ ብሎ የዛተው ሚሌ የሚባለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሎሌ የሆነው ነው። እንደሚለውም ከሆነ ለደሃው የተመደበውን የማህበራዊ ወጪ እንዳለ እንደሚሰርዝና የአሜሪካንንም ዶላር የመገበያያ ገንዘብ እንደሚያደርግ ነው ቃል ጊዳን የገባው። የገንዘብ ሚኒስተርም አድርጎ የሾመው ሰው ቀደም ብሎ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን የአርጀንቲናን ህዝብ ያደኸየና አገሪቱን በማራቆት በዎል-ስትሪት የባንክ ሰዎች ስር እንድትሽመደመድ ያደረገ ፀረ-ሰውና ፀረ-ተፈጥሮ፣ እንዲሁም ምንም ዐይነት ብሄራዊ ባህርይ የሌለው ሰው ነው። ይህ የሚያረጋግጠው ምንድነው? አሜሪካን በአርጀንቲናም ሆነ በሌሎች የደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ ራሴን ይጠቅመኛል ብላ ኮሙኒዝምን የሚጠሉ ጄኔራሎችንና ሌሎች መኮንኖችን ስልጣን ላይ በማውጣት ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደረገቻቸውና የገፋፋቺው ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ኢ-ህዝባዊ ፖለቲካዎች በእነዚህ አገሮች ውስጥ ቢያንስ የተገለጸለትና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የቆመ ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ኃይል እንዳይፈጠር በማድረጓ የመጨረሻ መጨረሻ ቀደም ብሎ በብራዚል ቦልሴናሮ፣ አሁን ደግሞ እጅግ አደገኛ የሆነ አርጄንቲናዊ ሜሊ የሚባል ሰው ስልጣን ላይ እንዲወጣ ለማድረግ በቅታለች። የየመንግስታቱ መኪናዎች የባሰ ውስብስብ በመሆናቸውና ለዘረፋና ለሙስና የሚያመቹ ሆነው ስለተዋቀሩ የፈለገው የፓርቲ ተወካይ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ላይ ቢወጣ ያለውንና የፈረጠመውን፣ ህዝቡን የባሰ የሚያደኸይውንና ስር የሰደድውን የማፊያና የድረግ ካርቴል በፍጹም ሊቋቋማውና ሊያስወግደው አይችልም። እንደነዚህ ዐይነት የህብረተሰብ ጠንቅ የሆኑ ማፊያዊ ድርጅቶች ከጸጥታው፣ ከፖሊሱና ከሚሊታሪው ጋር በጥቅም የተሳሰሩና እነሱም የሙስናው አንድ አካል በመሆናቸው ቁጥጥር ለማድረግና የመጨረሻ መጨረሻም ማስወገድ በፍጹም የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በአጠቃላይ ሲታይ አሜሪካን ከ1945 ዓ.ም በኋላ የበላይነትን ከተቀዳጀችበት ጊዜ ጀምሮ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ግልጽ የሆነ የመንግስታዊ አወቃቀር በሌላቸው አገሮች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆኑና በከፍተኛ ግፊትም ፍጻሜ እንዲኖራቸው የምታካሄዳቸው “የኢኮኖሚና የትምህርት ፖሊሲዎች” በሙሉ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ሰፋ ያለና ለማሰብ የሚችልና፣ የተሳሳቱ የህብረተሰብ አወቃቀሮችንና በኢኮኖሚ ሊበራሊዝም ስም ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮች የሚያስከትሏቸውን የተበላሹ ማህበራዊ፣ ኢኮሎጂያዊ፣ ባህላዊና የስነ-ልቦና ቀውሶችን ሊጠይቅና መፍትሄም ሊያፈልቅ የሚችል የህብረተሰብ ኃይል እንዳይፈጠር በማድረጓ ነው። በአሜሪካን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ ኤሊት ዕምነት ማንኛውም ህዝብን የሚጠቅም የኢኮኖሚ ፖሊሲና በዕውቀት አማካይነት ጭንቅላቱን የሚያድሰው ትምህርት በሙሉ ኮሙኒስታዊ ወይም ሶሻሊስታዊ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ወዲያውኑ በአንዳች መልክ መታገድ አለበት፤ ስልጣን ላይ የሚወጡ ህዝባዊ ባህርይ ያላቸውና አገር ወዳድ ኃይሎች ደግሞ በሚሊተሪ ኩዴታ መገልበጥ አለባቸው። ስለሆነም ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ የአሜሪካንና የተቀረውን የካፒታሊስት አገሮችን ጥቅም ወይም እነሱ የነፃ ገበያ ብለው የሚጠሩትን አስተሳሰብ የሚፃረሩ መሆን የለባቸውም። በዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ፣ ኢ-ተፈጥሮአዊና ኢ-ህብረተሰብአዊ አካሄድና፣ በነፃ ገበያ ስም የሚካሄደውም “የኢኮኖሚ ፖሊሲ” በካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ ያልታወቀና በሳይንስም ያልተረጋገጠ በመሆኑ በየአገሮች ውስጥ ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚያናጉ፣ በተለይም ደግሞ ደካማ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል መቆሚያና መቀመጫ የሚያሳጡ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው አገሮች በከፍተኛ የአገዛዝ ቀውስ ውስጥ እንዲወድቁ ለመደረግ በቅተዋል። በየአገሮች ውስጥ ያሉ ሀብቶችም ከ2-5% በሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥጥር ውስጥ ያሉና የውጭ ኃይሎችም እንዲመነዘብሩ አመቺ ሁኔታ ሰልተፈጠረላቸው እንደፈለጋቸው የሚንደላቀቁበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በየመንግስታቶች አውታር ውስጥ የሚገቡና ከፍተኛ ሹመት የሚሰጣቸው ከሀብታም ቤተሰብ የተወለዱና አሜሪካን ታላላቅ “ኤሊት ዩኒቨርሲቲዎች” ውስጥ የተማሩና በኒዎ-ሊበራል አገርን የማቆርቆዝና ህዝብን የማደኽየት የኢኮኖሚ ፓሊሲ የሰለጠኑ በመሆናቸው የሚያወጡትና ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሙሉ በአንድ በኩል ሀብታሙን የባሰ ሀብታም ሲያደርግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ደሃውን የባስ የሚያቆረቁዝ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ላይ ተደግፎ የማይንቀሳቀስ በመሆኑ የአገር ውስጥ ሀብት ወደ ውጭ እንዲፈስ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ህዝባዊ ሀብት(National Wealth) የሚፈጥር ባለመሆኑ በዚያው መጠንም ለስራ ፈላጊው የስራ መስክ ሊከፍት የሚችል አይደለም። ስለሆነም የስራ ዕድል ለማግኘት የማይችለው የግዴታ ወደ አልባሌ ስራዎች ላይ በመሰማራት ህይወቱ እንዲበላሽ ይደረጋል። የፖሊሲ አውጭዎችም አንድ አገር ከታች ወደላይ ኦርጋኒካሊ በሆነ መልክ እንዲገነባና ህዝብን በሚያስተሳስር በሁለንተናዊ ዕውቀት ወይም ደግሞ የሰብአዊነት ባህርይ ባለው የሰለጠኑ ባለመሆናቸው ተግባራቸው በሙሉ ህብረተሰቡን እንዳለ ማቆርቆዝና እያንዳንዱ ግለሰብ አምላክ የሰጠውን የማሰብ ኃይል እንዳይጠቀምና ፈጣሪ እንዳይሆን ማድረግ ነው። ስለሆነም እንደነዚህ ዐይነት በተወሰነ የአካዴሚክስ ትምህርት የሰለጠኑ ሰዎች ህብረተሰብአዊ ቀውስን ከመፍጠርና ህዝብን አቅመቢስ ከማድረግ በስተቀር የሚሰጡት ፋይዳ የለም።
ይህ ዐይነቱ ከፍተኛ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ መዛባት ግን በካፒታሊስት አገሮች፣ በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በታይዋን፣ በሲንጋፖርና በስካንዲኔቪያን አገሮች ውስጥ በፍጹም አይታይም። ታዲያ በእነዚህ አገሮች ውስጥ “በነፃ በገበያ” ስም ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ ሲሆን ለምንድነው እንደኛ ባለውና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው በሚጠሩት ውስጥ ከፍተኛ ማህበራዊ ውድቀትን ሊያስከትል የቻለው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ቀላል ነው። የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በልዩ ዐይነት የህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ በማለፋቸውና መንግስታትም ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የጣልቃ ገብ ፖሊሲ(Interventionist Policy) በመከተላቸውና የውስጥ ገበያቸውን በዕገዳ ፖሊሲ(Protectionist Policy) አማካይነት በመንከባከባቸው ነው። ይህ ዐይነቱ የየመንግስታቱ ጣልቃ-ገብነትና የዕውቅ ፖሊሲ ቀስ በቀስ በግለ-ሰብ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ አምራቾችና ነጋዴዎች አመቺ ሁኔታን ሊፈጥርላቸው ችሏል። በተለይም ደግሞ ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ የዕድገትና-የምርምር ማዕከል በማቋቋምና በመደጎም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩና በስራ ላይ እንዲውሉ ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ችለዋል። ይህ ዐይነቱ የየመንግስታቶች ድጋፍ በአብዛኛዎቹ የደቡብ አሜሪካና የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሚገባ ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይደለም።
ያም ተባለ ይህ በታሪክና በህብረተስብ ግንባታ ውስጥ እንደተረጋገጠው የአንድ አገርና ህዝብ ዕድል በተበላሸም ሆነ በጤናማ መልክ በጠቅላላው ህዝብ የሚወሰን ሳይሆን በተለይም ስልጣንን በተቆናጠጡ የሲቪሊና የሚሊታሪ፣ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ነው። ንቃተ-ህሊናቸው ከፍ ያለና ጭንቅላታቸው በጥሩ ዕውቀት የተገነቡ ኃይሎች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ከፊታቸው የተጋረዱና ማህበራዊ ሚዛናዊነትን የሚቀናቀኑ ወይም የሚጠሉ ኃይሎችን በመቋቋም ወይም በማስወገድ ከሞላ ጎደል ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅምና አገርን የሚያረጋጋ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ ነው። ለምሳሌ የሜጂ(Meiji) ዲይናስቲ በ1868 ዓ.ም ስልጣንን ሲጨብጥ ቀደም ብሎ ስልጣን ላይ የነበረውን ለንግድ እንቅስቃሴ ብቻ አትኩሮ የሰጠውንና ለሁለ-ገብ ዕድገት ጠንቅ የሆነውን የቶኮጋዋ(Tokugawa) ዲይናስቲ በማስወገድ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚሆኑ አዳዲስና ብሄራዊ ባህርይ ያላቸውን ወጣቶች በማሰልጠን ነው ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ማካሄድ የቻለውና የኋላ ኋላ ደግሞ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የበቃው። በአጠቃላይ ሲታይ በተለይም ከኋላ-መያዝ( Catch-up Development Policy) አለብን ብለው ከዝቅተኛ ደረጃ በመነሳት ሁለ-ገብ የሆነና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ አገዛዞች፣ ማለትም ጃፓን፣ ሶቭየት ህብረት ከ1917 ዓ.ም ጀምሮና በተለይም በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ የሆነው የኢንዱስትሪ ፖለቲካ፣ ዛሬ ራሺያ፣ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር፣ ዛሬ ደግሞ ቻይና የደረሱበትን የዕድገት ሁኔታ ስንመለከት በእነዚህ አገሮች ውስጥ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የታሪክን ተልዕኮ ለማሟላትና ህዝቦቻቸውን ለማስከበር ቆርጠው እንደተነሱ ማረጋገጥ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የአገር ወዳድነት ስሜት ብቻ በራሱ በቂ አይደለም። የአገር ወዳድነት ስሜት በከፍተኛ ዕውቀትና ጭንቅላትን በሚያድስ ሳይንሳዊ ዕውቀት የግዴታ መታገዝ አለበት።
የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ዕድገትን ሂደት ለመረዳት በታሪክ ውስጥ የምሁራንን ሚና ግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱ በጣም አስፈላጊ ነው። በሌላው ወገን ደግሞ የካፒታሊዝምን ዓለም አቀፋዊ የጥፋት ተልዕኮና ጭንቅላትን የማጨለም ወይም የመጋረድ ሚና ከስልጣኔ መፀነስና ማደግ ጋር እያነፃፀሩ ማየቱ ያለንበትን አስቸጋሪና የተወሳሰበ ሁኔታ ለመረዳት ያስችለናል የሚል ዕምነት አለኝ። ምክንያቱም ዛሬ ካፒታሊዝም እያልን የምንጠራው የኢኮኖሚ ስርዓት የፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስ ዕውቀቶች ባይፈጠሩና ቀስ በቀስም ባይዳብሩ ኖሮ ካፒታሊዝም የሚባለው ስርዓት ባልተፈጠረ ነበር። ይህ ማለት ግን የፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲስክ ዕውቀት አፍላቂዎችና ተመራማሪዎች ለካፒታሊዝም ስርዓት መታገል አለብን ብለው የተነሱ ነበሩ ማለት አይደለም። የእነሱ ዋና ዕምነት በጊዜው የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታና ጭፍን የሆነ የሃይማኖት ዕምነት ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት ስለሆነባቸው ሳይወዱ በግድ በዕውቀት ላይ በመረባረብ የአስተሳሰብ መድረኩ ሰፋ እንዲልና ዕድገትን በሚቀናቀኑ ኃይሎች ላይ ቀስ በቀስ ህብረተሰብአዊ ግፊት እንዲያይል አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቻሉ። ይህ በራሱ አዳዲስና ዘልቀ ለሚያስቡና ፈጣሪ ለሆኑ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ሊፈጥር ቻለ። ባጭሩ ካፒታሊዝም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በሙከራና በልምድ፣ ኋላ የቀሩ ኃይሎችን በማስወገድና ሰፊውን ህዝብ ደግሞ ከግብርና ስራው በማፈናቀልና ወደ ወዝአደርነት በመቀየር የተፈጠረ የአጋጣሚ ስርዓት ወይም ደግሞ በማርክሲስቶች አነጋገር የታሪክ ግዴታ የሆነ የኢኮኖሚ ስልተ-ምርት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች እንደሚሉን የካፒታሊዝም ስርዓት ቀጥ ያለ መንገድን በመከተል የተፈጠረ ሳይሆን ለስልተ-ምልቱ መፈጠር ቀደም ብለው የዕደ-ጥበብ ስራዎች ማበብ፣ እነዚህ ደግሞ በልዩ ስልት(Putting-Out System) መዳበርና በንግድ አማካይነትና በገንዘብ የልውውጥ ዘዴ ልዩ የሆነ ውስጣዊ ኃይል በማግኘትና በከተማዎች በዕቅድ በመሰራት አመቺ ሁኔታን በማግኘት ቀስ በቀስ በአድማስ እየሰፋ ሊመጣ የቻለ ስርዓት ነው። በሌላ አነጋገር፣ እነዚህ ሁሉ ቅድመ-ሁኔታዎች ባይመቻቹ ኖሮ የኋላ ኋላ የካፒታሊስት ስርዓት በአሸናፊነት ለመውጣት ባልቻለ ነበር። ይህም ማለት የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚለን የካፒታሊስት የገበያ ኢኮኖሚ በጠያቂና በአቅርቦት(Demand & Supply) መሀከል በሚደረግ የንግድ ልውውጥ የተፈጠረ ሳይሆን ሰፊውን ህዝብ ከቀየው በማፈናቀልና በተፈጥሮ ላይ በከፍተኛ ደረጃ በመዝመት ቀስ በቀስ እየዳበረና ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ነው። የኢንዱስትሪ አብዮትና የካፒታሊዝም ዕድገት በስምምነት እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ የደረሱ ሳይሆን በአፍላው ወቅት ላይ ሰፊውን ህዝብ ወደ ድህነት ዓለም በመገፍተርና ተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ በመጻረር ቀስ በቀስ በእልህ አስጨራሽ ትግል እየተገራና ከሞላ ጎደል ማህበራዊ ባህርይ እንዲይዝ የተደረገ ስርዓት ነው። ይህም ማለት በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካን የካፒታሊስት ስርዓት ዕድገት ውስጥ ኃይል የማይናቅ ሚናን ተጫውቷል፣ ተፈጥሮም በከፍተኛ ደረጃ ተናግቷል፤ ወደ ውጭ ደግሞ የካፒታሊስት ስርዓት በወረራና በዝርፊያ እየደለበ የመጣና ቀስ በቀስም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ የቻለ የኢኮኖሚ ስልተ-ምርት ነው ማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ ሲታይ የስልጣኔን ታሪክ ስንመረምር አገሮች አንደ ህብረ-ብሄር ከመመስረታቸው በፊት ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ማቲማቲክስና ሌሎች ለዕድገት የሚያስፈልጉ መሰረተ-ሃሳቦች ሁሉ ሊፈልቁ የቻሉት ልዩ የመንፈስ ኃይል ባላቸውና የሰውን ልጅ ከጨለማ ማውጣት አለብን ብለው በከፍተኛ ደረጃ ጭንቅላታቸውን በማስጨነቅ ጊዜያቸውን በሰዉ ልዩ ኃይሎች አማካይነት ነው። በጊዜው ሰፊ ዕውቀትን መሰረት አድርገው የተነሱ ጥቂት ሰዎች በነበረው የአኗኗር ስርዓትና የጦርነት ባህል ባለመደሰታቸውና፣ የሰውም ልጅ በእንደዚህ ዐይነት አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ መኖር የለበትም ብለው አጥብቀው በመገንዘባችውና፣ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ዕውቀትን በማፍለቅ ላይ ለማዋል በመቻላቸው ብቻ ነው። ስለሆነም የግሪክ ስልጣኔ የተጀመረው በጥቂት በጊዜው የተፈጥሮ ፈላስፎች ተብለው በሚጠሩ እንደታለስ በመሳሰሉ ልዩ ዐይነት ተልዕኮ ባላቸው ሰዎች አማካይነት ነው። የኋላ ኋላ ደግሞ እንደሶክራተስና ፕሌቶ የመሳሰሉት ታላላቅ ፈላስፋዎች ሲነሱ ዋናው ተግባራቸውም የኮስሞን ህግ በማጥናት ለምን የሰው ልጅ እንደኮስሞስ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ኑሮውን አያደራጅም? ለምንስ በጦርነት ኃይሉን ይጨርሳል? ምን ምን ነገሮች ናቸው ጭንቅላቱን ቆልፈው የያዙት? ለምንድነው የሚኖርበትን አካባቢ ስርዓት ባለው መልክ የማያዋቅረውና ከዚህ በመነሳት ልዩ ልዩ ነገሮችን በመፍጠር እንደማህበረሰብ ለመኖር የማይችለው? በማለት ሰፋ ያለ የምርምር መሰረት በመጣልና ለተከታታዩ ትውልድ በማስተላለፍ ነው። ይህ የጭንቅላት ምርምራቸውም ከፍልስፍና በማለፍ ወደ ተግባራዊ ለመመንዘርና፣ የኋላ ኋላ ከተማዎችና የስፖርት መዝናኛ ቦታዎች፣ እንዲሁም የዕደ-ጥበብና የንግድ እንቅስቃሴዎች በመዳበር በጊዜው ተዝረክርኮ ይኖር የነበረውን ህዝብ በዚህ አማካይነት በማስተሳሰር እንደማህበረሰብ እንዲኖርና ራሱንም እንዲያውቅ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ዐይነቱ የማህበረሰብ አመሰራረት በተለያዩ አገሮችም ቀደም ብሎ የታየ ቢሆንም የግሪክ ፈላስፎች ናቸው ፍልስፍናና ሳይንስን ወደ ውጭ በማውጣት የሰው ልጅ በአርቆ የማስብ ኃይሉ አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር አዲስ የኑሮ ሁኔታን ለመመስረት እንደሚችል ያስመሰከሩት ማለት ይቻላል።
የኋላ ኋላ የግሪኩን ስልጣኔ መልሶ ማግኘት በመባል የሚታወቀው የሬናሳንስ አፀናነስም በጥቂት ሰዎች፣ በመጀመሪያ በአንድ ሰው፣ ዳንቴ በመባል የተፀነሰና የኋላ ቀስ በቀስ በተከታታዩ ትውልድ የተቀጣጠለ የመንፈስን ተሃድሶ መሰረት በማድረግ ወደ ተግባራዊነት የተለወጠ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ዘመን ነው በጣሊያን ምድር በአንዳንድ ቦታዎች የዕደ-ጥበብ ስራዎችና ንግድ ማበብ የቻሉት። በዚህ ዘመን ነው የህንፃ አሰራሮች መንፈስን እንዲያድሱ ሆነው በተወሰኑ የጂኦሜትሪ ቅርጾች መልክ ለመሰራት የቻሉት። ይህ ዐይነቱ የከተማዎች ዕድገት፣ የዕደ-ጥበብ ማደግና የንግድ እንቅስቃሴ መዳበር እንደ ጋሊሌዮ ጋሊሊዬ፣ ሊዮናርዶ ዳቪንቺና ለሚካኤል አንጀሎና ለሌችም የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስ ተመራማሪዎች አመቺ ሁኔታን በመፍጠር ነው በጣሊያን ምድር ዐይነተኛ ለውጥ ሊመጣ የቻለው። በዚህ ወቅት ይህ ዐይነቱ የጭንቅላት ስራና ፈጠራ እየተካሄደ ባለበት ዘመን እዚያው በዚያው የፖለቲካን ስልጣን የተቆናጠጡ ኃይሎች በዚህ ስልጣኔና ዕድገት ሳይመሰጡ ይሰሩ የነበረው ስራ ርስ በርስ መጋጨትና አሻጥር መስራት ነበር። ይህ ዐይነቱ የአሻጥር ፖለቲካ በተለይም በፊዩዳሉ ስርዓት ዘፍቀው በሚገኙ አገሮች እንደጀርመን ለመሳሰሉት የዕድገት እንቅፋት በመሆን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ ነው የህብረ-ብሄር ምስረታ ዕድል ማግኘት የቻሉት። ይህም ሊሆን የቻለው በጊዜው ጀርመን የነበረችበትን ሁኔታ በሚገባ የተረዱና ከኋላ-ቀርነት ካልተላቀቀች በቀላሉ በውጭ ኃይሎች የመጠቃት ዕድል ያጋጥማታል ብለው በተነሱና፣ ለሳይንስና ለጥበብ ቅድሚያ በሰጡ ጥቂት በተገለጸላቸው ኃይሎች አማካይነት ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ በአውሮፓ ምድር በሁለት ኃይሎች መሀከል በተከታታይ ብዙ ዓመታቶችን ያስቆጠረ ትግል ተካሂዷል። አንደኛው ኃይል የግዴታ በድሮውና በአረጀው የአኗኗር ስልቱ መኖር አለብኝ በማለትና የሊበራል አስተሳሰቦችን በሙሉ ሲዋጋ፣ የተቀረው ኃይል ደግሞ የግዴታ በአረጀው የአኗኗር ስልት መኖር የለብኝም ብሎ ቆርጦ በመነሳት የኋላ ኋላ በአሸናፊነት የወጣበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ይህ ዐይነቱ በከበርቴው የህብረተሰብ ክፍል የተጠናቀቀው የሪፓብሊካን አስተሳሰብ፣ ማለትም ግለሰብአዊ ነፃነትን ማወቅና የህግ የበላይነትን መቀበል የግዴታ በአዳዲስ የሳይንስና የማቲማቲክስ ግኝቶች በመደገፍ፣ በዚህም አማካይነት የተሟላ ዕድገት እንዳይተገበር ተቀናቃኝ የሆኑ ኃይሎችን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አሽቀንጥሮ የጣለበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሲሆን፣ የህብረተሰብ ዕድገትም የኋሊት ጉዞ መሆኑ ቀርቶ ወደፊት የሚጓዝና በሳይንሳዊ ምርምር አማካይነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚፈጠሩበትና ወደ ተግባር የሚመነዘሩበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደቻለ መገንዘብ ይቻላል። አዲስ የተፈጠረውም የአመራረት ስልትና የንግድ እንስቃሴ በአዳዲስ ቲዎሪዎችና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በመደገፍ የከበርቴው መደብ የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ አስችለውታል ማለት ይቻላል። የእነ አዳም ስሚዝን The Wealth of Nations መመልከቱ ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ደግሞ የኋላ ኋላ ካፒታሊዝም ተግባራዊ የሆነባቸው እንደ አሜሪካን በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ሂደቱ የበለጠ አረመኔያዊና፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝቦችን በመግደልና፣ ጥቁሩን አሜሪካዊ ደግሞ በፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማሰማራትና፣ በከፍተኛ ደረጃ በማሰቃየትና የመማርና የማውቅ ዕድል እንዳያገኝ በማድረግ ነው። የአሜሪካን ካፒታሊዝም እንደ አውሮፓው በሶስት ጭንቅላትን በሚያድስ የተሃድሶ ጉዞ ውስጥ ለማለፍ ባለመቻሉ ይኸው እንደምናየው በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገት ቢኖረውም፣ በሌላ ወገን ግን የፖለቲካ አወቃቀሩ ኢ-ዲሞክራሲ፣ ኢ-ሰብአዊና፣ የበለጠ የነጩ የኦሊጋርኪ መደብ የበላይነት እንዲኖረው ሆኖ የተዋቀረ በመሆኑ ከ1945 ዓ.ም በኋላ በበላይነት ሲወጣ ይህንን የበላይነቱንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ይችል ዘንድ አዳዲስ ዘዴዎችን መፍጠር ቻለ። ይህም ማለት የአሜሪካን ካፒታሊዝም የበላይነቱን ይዞ ለመቆየት የሚችለው በየአገሮች ውስጥ አፈቀላጤዎችንና ታዛዦችን ሲመለምልና በእነዚህ አማካይነት የሌሎችን አገሮች ዕድገት ሲቀናቀንና፣ ወደ ርስ በርስ ጦርነትም ውስጥ ሲከታቸው ብቻ ነው። ይህም ማለት ጦርነት በራሱ የካፒታሊዝም አንዱ አካል የሆኑና የሀብት ማከማቻም ዘዴ ነው ማለት ይቻላል። በየቦታው ጦርነት ሲቀሰቀስና ብዙ ምስኪን ህዝብ ሲገደል የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎችም አክሲዮን ዋጋ ከፍ እያለ ይመጣል፤ በሰው ደም የትርፍ ትርፍ ያገኛሉ ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ ያልተገለጸለትና በከፍተኛ የስለላና የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ የሚገለጽ ስርዓት እንደምናየው አሜሪካን የበላይነትን ተቀዳጀ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በየአገሮች ውስጥ እየገባ ዕድገትን የሚቀናቀን አደገኛ የስልጣኔ ጠንቅ ለመሆን ችሏል። በሌላ ወገን ደግሞ እዚያው በዚያው በከፍተኛ ደረጃ የተገለጸለት የሳይንስ ኮሙኒቲ የህብረተሰብ ኃይል ያለበት አገር እንደሆነ እንመለከታለን። በዚህም ምክንያት የተነሳ በክፍተኛ የጭንቅላት ስራ የሚጻፍ የፍልስፍና፣ የሶስዮሎጂ፣ የኢኮኖሚክስና የሳይንስ መጽሀፎችና ግሩም ግሩም የስነ-ጽሁፍ ስራዎች የሚፈልቁት በአሜሪካን ምድር ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የጭንቅላት ውጤትና የተገለጸለት ስራ በአሜሪካን የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ ኤሊት ጭንቅላት ውስጥ ዘልቆ የገባና ሰብአዊም እንዲሆን ያደረገው ሳይሆን ይባስ ብሎ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን በመስራት አልገዛም ያሉ አገሮችንና አገዛዞችን የሚጨፈጭፍበትና ህዝቦችንም በልዩ መርዝ የሚገድልበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህም የሚያረጋግጠጠው የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ ኤሊቱ በራሱ ዓለም የሚኖርና እንዴት አድርጌ የዓለምን ህዝብ በጦርነት መንፈስ ውስጥ እንዲጠመድ ማድረግ አለብኝ ብሎ የሚቅበዝበዝና የየራሱን ቡችላዎች በመኮትኮት ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የቻለ በጣም አደገኛ የሆነ ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ዛሬ በተለያየ መልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጦርነቶች ናቸው ማለት ይቻላል። እዚህ አውሮፓ ምድርም በራችን ላይ በራሺያና በዩክሬይን መሀከል የሚካሄድው የወንድማማቾች ጦርነት በመሰረቱ የአሜሪካንና የግብረ-አበሮቹ በውክልና መልክ የሚካሄድ ጦርነት ነው። ይሁንና ግን ይህ ጦርነት እንደነ ፑቲን በመሳሰሉ ጠንካራና አገር ወዳድ መሪዎችና አዳዲስ የጦር መሳሪያ ፈጣሪዎች እየተደመሰሰና አሜሪካንና ግብረአበሮቹ የሚያደርጉትን እንዳጡና ግራ እንደገባቸውም እንመለከታለን። በጣም ደደብ በሆነው በሲሌንስኪ የሚመራው የዩክሬይን አገዛዝ የአቶም ኃይል ከሆነው ከጎረቤት አገሩ ጋር የግዴታ ግብግብ መግጠም አለብኝ፣ የማካሄደውም ጦርነት የአውሮፓንና የአሜሪካንን ነፃነት ለመጠበቅ ነው በማለት የሚያካሂደው ጦርነት ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ የዩክራይንን ህዝብ ህይወት እንደቀጠፈ ይነገራል። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣት ወታደሮች ህይወታቸውን እንዲሰው ተደርገዋል። ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ወደ ተለይዩ አውሮፓ አገሮችና አሜሪካ ለመሰደድ ተግድደዋል። ወደ 600 ሺህ የሚጠጉ ለጦርነት ሊመለመሉ የሚችሉ ወጣቶች ሸሽተው በመውጣት በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው ስልጣንን የጨበጡ ጥቂት ኃይሎች የአንድን ህዝብና አገር ዕድል በዚህ መልክ ለመወሰን እንደሚችሉ ነው። በዚህ መልክ አንድ አገር ታሪክ የሚሰራባትና ህዝብም የሰለጠነ ኑሮ እንዲኖርባት ከማድረግ ይልቅ እንዳለ ወደ ጦርነት ቀጠና በመለወጥ የብዙ መቶ ዐመታት የታሪክ ስራዎች እንዲፈራርሱ ለመደረግ በቅተዋል። ብዙ የሚያማምሩ ከተማዎች እንዳእል ወድመዋል። ጭንቅላታቸው በተመረዘ መሪዎች የምትመራ አገርና ህዝብ የመጨረሻ መጨረሻ ዕጣቸው ሞት፣ መሰቃየትና መሰደድ፣ እንዲያም ሲል ጠቅላላው ቤተሰብ እንደሚበታተን ነው ይህ ዐይነቱ የተበላሸ ፖለቲካ የሚያረጋግጠው። ለዚህ ነው ታላቁ ፈላስፋ ፕሌቶ ፖለቲክኞች የግዴታ ፈላስፋዎች መሆን አለባቸው፤ አሊያም ደግሞ ፖለቲከኞች በፈላስፋዎች መመከርና መጠምዘዝ አለባቸው የሚለው። በፕሌቶ ዕምነት ጭንቅላቱ በፍልስፍና ዕውቀት የዳበረ ሰው ብቻ ነው አርቆ ማሰብ የሚችለውና በህዝቡ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ለማድረግ የሚችለው።
ያም ተባለ ይህ የየአገሮችን ዕድገትና ውድቀት ስንመለከት የአንድ አገርና ህዝብ የማደግና ቆርቁዞ የመቅረት ዕድል ሊወሰን የሚችለው በየአገሩ በሚኖረው ሰፊው ህዝብ አማካይነት አይደለም። በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ የአንድን ህዝብ ዕድል በመጥፎም ሆነ በጥሩ ነገር ሊወስኑና አገራችውን እንዲራከስም ሆነ እንዲከበር የሚያደርጉት ጥቂት ሰዎች ናቸው። ያልተገለጸላቸው ሰዎች ስልጣንን በያዙበት አገርና ከፍተኛ ምሁራዊ ክፍተት ባለበት አገር ውስጥ አንድ ህዝብ የመዋረድና አገርም የመፈረካከስ ዕድል ያጋጥማታል። በሌላ ወገን ደግሞ ጭንቅላቱ በደንበ በዳበረና የታሪክ ኃላፊነትን የተገነዘበ ኃይል ስልጣን ላይ የሚወጣ ከሆነ አንድ አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ የማደግ ኃይሏ ከፍ ይላል፤ ህዝቧም ይከበራል። በሚገባ እንደተረጋገጠውና፣ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ኤሊቶች ጭንቅላት ውስጥ ግንዛቤ ያላገኘው ነገር የመንፈስ ተሃድሶ ባልተካሄደባቸው አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ሁለ-ገብ ዕድገት ሊመጣ እንደማይችል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ቻይና፣ እንደ ጃፓን፣ ኮሪያና ሲንጋፖር በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የሚታየው ሁለ-ገብ ዕድገት በአውሮፓው ዐይነት የመንፈስ ተሃድሶ የተደገፈ ሳይሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ በሰፈነው ልዩ ዐይነት የጭንቅላት አወቃቀርና የስራ ልምድ ምክንያት የተነሳ ህዝቦችን በማስተባበርና በዲሲፕሊን እንዲታነጹ በማድረግ ከሞላ ጎደል ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ዕድገት ሊፈጠር እንደቻለ እንመለከታለን። በተለይም የቻይናን የዕድገት ታሪክ ስንመለከት ቪትፎገል የሚባለው የህብረተሰብ ሳይንስና የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ The Oriental Despotism በሚለው መጽሀፉ ውስጥ በቻይና ውስጥ ከሶስት ሺህ ዐመታት በላይ በሰፈነው ሰፋ ያለ ቢሮክራሲያዊ መዋቅርና ሰፊውን ህዝብ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች እያንቀሳቀሱ ማሰራት የቻይንና ህዝብ መንፍስ በዲሲፕሊን እንዲታነጽ እንዳደረገውና፣ የኋላ ኋላም በተለያዩ ነገሮች የሚገለጽ እንደ ኬራሚክ፣ የጥይት ባሩድ፣ የወረቀት ስራና ሌሎችም የዕድገት መገለጫዎች መሰረት እንደጣለ ያስረዳል። ይህ ዐይነቱ ዲስፕሊናዊ የህዝብ መተሳሰርና ስራን ማክበር የኋላ ኋላ እነ ማኦ ሴቱንግ በ1949 ዓ.ም ስልጣንን ሲጨብጡ እንደመነሻ እንደሆናቸውና፣ አንዳንድ ስህተቶች ቢሰሩም ጥናቶች ሁሉ እንደሚያረጋግጡት ካለዚህ ዐይነቱ የእንስቃሴና ድርጅታዊ ስራ ቻይና ዛሬ ወደ ሚታየው በሳይስንና በቴክኖሎጂ ወደ ሚገለጸው ዕድገት ላይ ለመድረስ እንደማትችል ነው።
ወደ ተቀሩት የአፍሪካ አገሮችና ወደ አገራችን ስንመጣ ሂደቱ ለየት ያለ ነው። በባሪያ ንግድና በቅኝ ግዛት አስተዳደር የተነሳ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ዕድገት ሊጨናገፍ ችሏል። የአውሮፓውያን የባሪያ ነጋዴዎችና የቅኝ ግዛት አስተዳዳሪዎች ወደ አፍሪካ ምድር ብቅ እስካሉበት ጊዜ ድረስ አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች በስራ ክፍፍል፣ በንግድና በከተማዎች ዕድገት የሚገለጽ የዕድገት ሁኔታ እንደነበራቸው ወደ አውሮፓ ተዘርፈው በመጡ የታሪክ ቅርሶችና በየሙዜዬሞች ውስጥ በሚታዩት የሚገለጽ ነው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ አፍሪካውያን ታሪክና ስልጣኔ አልነበራቸውም የሚባለው አነጋገር በምንም ዐይነት ማረጋገጫ የሚደገፍ አይደለም። ከቅኝ ግዛት ከተላቀቁ በኋላስ ለምን ልዩ ዐይነትና ወደ ውስጥ ያተኮረ ዕድገት ለማሳየት አልቻሉም? ለሚለው በቀላሉ በሙስናና በዘረፋ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። አውሮፓያውያን የቅኝ ግዛቶቻቸውን ለቀው ሲውጡ ሁኔታዎችን ስላበላሹና በዚያው የብዝበዛ ስርዓት እንዲቀጥል የመንግስት አወቃቀሮችን ስላደራጁ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም። የለውጥ ሙከራ በተካሄደባቸው እንደ ኮንጎ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ እንደ ፓትሪስ ሉቡምባ የመሳሰሉት የተገለጸላቸው መሪዎች በሲአይኤ በተቀነባበረ ሴራ በራሱ ሰው እንዲገደል ለመደረግ በቅቷል። የእነ ዶክተር ኩዋሜ ንክሩማም ዕጣ ከዚህ ያነሰ አይደለም። በዚህ መልክ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ መሰረታዊ ለውጥን ለማጨናገፍ ሲባል በውጭ የስለላ ድርጅቶች አማካይነት ከስድሳ በላይ የሚቆጠር የመንግስት ግልበጣዎች ተካሂደዋል። ከዚያም በኋላ አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና መሪዎቻቸው በሳይንስ ያልተደገፈና ሁለ-ገብ ዕድገትን የሚቀናቀን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ተግባራዊ በማድረጋቸው ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትን ከማስፋፋትና ሀብት ከመዝረፍ ያለፍ ሊሆን አልቻለም። በዚህ ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብቶች ቢኖራቸውም በዕዳ እንዲተበተቡና የንግድ ሚዛናቸውም በከፍተኛ ደረጃ እንዲናጋ ለመደረግ በቅቷል። ይህ ሁኔታም በቀላሉ ሊለወጥ የሚችል አይመስልም።
ወደ አገራችን ስንመጣ የድሮውን ታሪክ ወደ ኋላ በመተው በተለይም ከ1940ዎች አጋማሽና 1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተፈጠረው ትውልድ በተበላሸ የትምህርት ስርዓትና በፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ምክንያት የተነሳ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ዕድገትን የተገነዘበና ለዚህም ዝግጅት ለማድረግ ያልቻለ ነው። በአብዮቱ ወቅት ሰፊውን ህዝብ የማስተባበርና የማደራጀት ዕድል ቢኖርም ይህንን በጣም ጥሩ አጋጣሚ ለመረዳት ያልቻለው የተወሰነው ኃይል ስልጣን ቶሎ መያዝ አለብኝ ብሎ በመቻኮሉና ወደ አላስፈላጊ የመሳሪያ ትግል ማምራቱ በቀላሉ ልንወጣ የማንችለው ማጥ ውስጥ ሊከተን ችሏል። በጊዜው የነበረው በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የተካፈለውና መሪ ነኝ የሚለው የተወሰነው ክፍል የፖለቲካ ትርጉምን የተረዳ አልነበረም፤ በጊዜው የነበረውን ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊና ለመረዳት ባለመቻሉ በህብረተሰባችን ውስጥ ያለውን የተለያየ ቅራኔዎች ለማስተናገድና ህዝቡን ጥበባዊ በሆነ መልክ በመያዝና በማደራጀት ከሞላ ጎደል አብዮቱ ትክክለኛውን ፈር እንዲይዝ ለማድረግ አልቻለም። በዚህ ዐይነቱ የትርምስ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የተገለጸለትና ሰፊውን ህዝብ የሚያስተባብር ኃይል ብቅ ማለት በፍጹም አልቻለም። ሰፋ ያለ ዕውቀትም ሊዳብር አልቻለም። ሁሉም ነገር ወደ ጦርነት ላይ በማተኮሩ ለአገር ዕድገት የሚውለው ንብረትና ኃይል እንዲወድም ለመደረግ በቃ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የውስጥ ፀረ-የዕድገት ኃይሎች ከውጭ የስለላ ኃይሎች ጋር በመተባበር የተገለጸላቸውን ኃይሎች ማሳደድና መግደል ነበር ዋናው ተግባራቸው። ይህ ሁኔታ የግዴታ ደርግን የባሰ ወደ አምባገነንነት ሲመራው፣ በዚያው መጠንም በነጻነት ስም የሚንቀሳቅሱ ያልተገለጸላቸው ደንቆሮ ኃይሎች ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ ኃይሎች በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ ስልጣንን ከጨበጡ በኋላ በከፍተኝ ፍጥነት ነው በምዝበራ ስራ ውስጥ በመሰማራት በአገራችን ምድር የሞራል ውድቀት እንዲፈጠር ለማድረግ የበቁት። ይህ ዐይነቱ የሞራል ውድቀት በራሱ ደግሞ ልዩ የሆነን የህብረተሰብ ኃይልን በመፍጠር ይህ ኃይል ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ በውጭ ኃይሎች በመታዘዝና በመደገፍ በጠቅላላው ህዝባችን ላይ ጦርነት በመክፈት አገራችንን ወደ ጦርነት ቀጠና ውስጥ ለመለወጥ እንደቻለ እንመለከታለን። ይህ በራሱ የሚያረጋግጠው በአገራችን ምድር የታሪክን አደራ ለመቀበል የሚችልና የሞራል ኃላፊነት የሚሰማውና ለሁለ-ገብ ዕድገት ታጥቆ የሚሰራ መንፈሱ የታደሰና የተገለጸለት ኃይል ብቅ ማለት እንዳልቻለ ነው። በተጨማሪም ሁኔታው የሚያረጋግጠው በአገራችን ምድር የፖለቲካ ተዋንያን ነን የሚሉ ኃይሎችና ድርጅቶች ተልዕኮዋቸው አገርን በጸና መሰረት ላይ መገንባት ሳይሆን የውጭ ኃይሎችን አገርን የማፈራረስ አጀንዳ አስፈጻሚዎች በመሆን ቀና ደፋ እያሉ እንደሚሰሩ ነው። ይህ በራሱ ደግሞ የሚያረጋግጠው እነዚህ ድርጅቶችና አንዳንድ ግለሰቦች ፖለቲከኛ ነን ብለው ቢጮኹም የፖለቲካን ትርጉም አለመረዳታቸው ብቻ ሳይሆን ጭንቅላታቸውም የቀጨጨ መሆኑን ነው ከእንቅስቃሴያቸው የምንረዳው። ስለሆነም ሳይንሳዊ ትንተናን ለመስጠት የማይችሉና ህዝብን በማደናገር የጨለማውም ዘመን እንዲራዘም የሚያደርጉ ናቸው። አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲሁም ጠቅላላው የመንግስት አወቃቀር የዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ፣ ኢ-ተፈጥሮአዊና ኢ-ህብረተሰብአዊ ሂደት ውጤቶች ናቸው። በአለፉት ሰባ ዓመታት በአገራችን ምድር የባህል ተሃድሶ ለመካሄድ ባለመቻሉ የግዴታ እንደ አቢይ አህመድ የመሳሰሉ የአገርንና ህዝብን የሚያተረማምሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ብቅ ለማለት ችለዋል። በሌላ አነጋገር ሰዎቹ ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆን ከህብረተሰብአችን ውስጥ የፈለቁ ናቸው። በአጉል ትረካና በዝቅተኛ ስሜት በመታገዝ በአጭ ኃይሎች በመታገዝ አገራችንን ወደ ጦር አውድማነት ለመለወጥ የቻሉ ናቸው። የውጭው ኃይልም ይህንን ደካማ አስተሳሰባቸውን ስለተረዳ በዚያው አገርን የማተረማመስና ለመገንባትና ለማስተዳደር እንዳይቻል እንዲቀጥሉበት እየገፋፋቸው ነው።
ለማንኛውም የዛሬው በአብይ አህመድ የሚመራው ፋሺሽታዊ አገዛዝ የግዴታ መወገድ ያለበት ቢሆንም፣ አገራችንና ህዝባችን ተመልሰው ወደ ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገቡ ከተፈለገ የግዴታ የተገለጸለትና በራሱና በህዝባችን ላይ የሚተማመን ልዩ ኃይል ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ ኃይልም እስከዛሬ ድረስ የዘለቀውን በህዝባችን ላይ በውስጥ በዘቀጡ ኃይሎችና በውጭ ኃይሎች ተባባሪነት የደረሰውን ዕልቂትና የሞራል ውድቀት በደንብ የተረዳና በሰፊውም ለመተንተን የሚችል መሆን አለበት። በሌላ ወገን ግን በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያለውን በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚለውንና፣ እዚህና እዚያ የሚራወጠውን ኃይል ስመለከት መቶ በመቶ ማለት ይቻላል ያልተገለጸለትና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ኃይል የሆነ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ በመሪነት ደረጃ ራሱን አጉልቶ የወጣና ታከታዮቹም ዕድገት ማለት ምን ማለት ነው? የሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋቶችስ እነማናቸው? የሚሉትን መሰረታዊና አስፈላጊ ነገሮች የተገነዘበ አይደለም። ለአገር ግንባታ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ልዩ ልዩ ዕውቀቶች ጋርም የተዋወቀ አይደለም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ ኃይል ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ ከምን መጀመር እንዳለበት የሚያውቅ አይደለም። በተለይም ስለፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ያለው ዕውቀት ግልጽ አይደለም። ስለሆነም በተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መሀከል ያለውን ልዩነት በሚገባ የተከታተለና እስካሁንም ድረስ በጥናት መልክ ለውይይት ያቀረበው ነገር የለም።
ከዚህም በላይ በፖለቲካ ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸረበውንም ሴራ ለመረዳት የሚፈልግ አይደለም። ለፖለቲካ ትግል መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ለምሳሌ ግሎባል ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ከሚባሉ ጽንሰ-ሃሳቦች ጋርም በፍጹም የሚተዋወቅ አይደለም። እነዚህን ጽንሰ-ሃሳቦች በሚገባ መረዳት ደግሞ የቱን ያህል ለዕውነተኛ ነፃነትና ዕድገት በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። በአጭሩ ለፖለቲካ ስልጣን የሚደረገው ትግል ከነፃነትና፣ የግዴታ ደግሞ ከተሟላ ወይም ከሁለ-ገብ ዕድገት ጋር የተያያዘ መሆኑን የተረዳ ኃይል በአሁኑ ጊዜ አለ ብሎ ለመናገር በፍጹም አይቻልም። ስለሆነም ያለው አማራጭ ይህንን ዐይነቱን ግድፈት መቅረፍ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ኃላፊነት ደግሞ በአረጀው ትውልድ ላይ የሚወድቅ ሳይሆን በታዳጊውና በአሁኑ ሰዓት ዕድሜው በሃያዎቹ ውስጥ በሚገኘው ትውልድ ብቻ ነው። ያረጀው ትውልድ ጭንቅላቱ አዳዲስ ነገሮችን ለማፍለቅም ሆነ ለመቀበል ስለማይችል ኢትዮጵያዊነት ከማለት በስተቀር የሚለግሰውና የሚያሳየው ብሩህ የዕድገት ፈለግ የለም። ምክንያቱም ቀላል ነው። የአብዛኛዎቻችን ጭንቅላት በተሳሳተ የአካዴሚክስ ትምህርት የተቀረጸ ስለሆነ የአንድን ህብረተሰብና የዓለምን ሁኔታ ከተለያዩ አንፃሮች የመመርመርና መፍትሄም የመስጠት ልምድና ችሎታም የለንም። በሳይንስ ዓለም ውስጥ ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቹ መሰረተ-ሃሳቦችና መመሪያዎች ስላሉ አብዛኛዎቻችን ከእነዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ዕውቀቶች ጋር የምንተዋወቅ አይደለንም። የነገሮችንም ሂደትና ሁኔታዎች በቁንጽል ተለያይተው እንደሚገኙ ስለምንረዳ ዕድገት ሲባል ኦርጋኒክ ወይም የተያያዘ የሆነና፣ ለዚህ ደግሞ ከመንግስታዊ አወቃቀር፣ ከፖለቲካ ኤሊቱ የዕውቀት መሰረት ሁኔታ በመነሳት ይህንን በማረም ሁለ-ገብ ወደሆነ የተቋማት ግንባታና፣ ህዝብን ወደሚያሳትፍ፣ ወደየሚያነቃ፣ ወደሚያደራጅና፣ በራሱ እንዲተማመን ወደሚያደርግ ሁኔታ ለማምራት ያለን ዕውቀት በጣም ውስን በመሆኑ ይህንን ዐይነቱን ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያመቸውን ሂደት ከመጀመሪያውኑ አጥብቀን እንቃወማለን። በውስጥ ኃይሎች ከመተማመን ይልቅ የውጭ ኃይሎችን ምክር ለመስማት እንጣደፋለን። ባጭሩ በራሳችንና በህዝባችን፣ እንዲሁም ባሉን ጥቂት ምሁራዊ ኃይሎች ለመተማመን አንችልም፤ አንፈልግምም። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች የግዴታ በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑና፣ ሰፊውን ህዝብ በማንቃትና በማደራጀት አዲስና የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር የሚችሉ አገር ወዳድ ኃይሎች መሆን አለባቸው። መልካም ግንዛቤ!!
ማሳሳቢያ፤ ኢትዮጵያችንና ህዝባችን ከእንግዲህ ወዲያ የዝቃጮችና የውጭ ኃይሎች አሽከር በሆኑና
መንፈሳቸው በተሳከረ መጨፈሪያ መሆን የለባትም !!