[gtranslate]

ከጁንታው ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያችንን ለሚያተራምሱ የነጭ ጁንታዎችን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ልንታገላቸው ይገባናል!! ብራቦ አቶ ኦባንግ-እኛ ለመናገር የማንፈልገውን በግልጽ ቋንቋ ስለተናገርክ!!

                                                                                               ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                             18.01.2021

 

መግቢያ

ከአንድ ወር ተኩል በፊት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል፣ በትግራይ በሰፈረውና ብዙ ዓመታትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ወታደር ላይ ወያኔ ጨለማን ተገን አስታኮ የከፈተው ጠርነትና የገደላቸው ወታደሮቻችንን በሚመለከት ሁላችንንም አስቆጥቶናል። ከዚያ በኋላም ጀግናው ወታደራችን፣ በአማራው የክልል ኃይልና በፋኖዎች እየታገዘ ያካሄደው ህግን የማስከበርና የትግራይን ክልል ከፋሺሽቱ የወያኔ ቡድን ለማስለቀቅ ያደረገው ትግልና ያስቆጠረው ድል ሁላችንንም አስደስቶናል። የወያኔ በማያዳግም ሁኔታ መደምሰስ በአገራችን ምድር አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍና የኃይል አሰላለፍ፣እንዲሁም ደግሞ የፖለቲካ ሁኔታ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ ሲታይ ወያኔ በአሁኑ አጠራር ደግሞ የጥቁር ጁንታ የሚል የመጠሪያ ስም የተሰጠው በወታደሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በማይካድራ የፈጸመው ፋሺስታዊ ድርጊት አብዛኛዎቻችንን አበስጭቷል። ይህ ድርጊቱ ብቻ ሳይሆን ፋሺሽታዊ የሚያሰኘው ለመቁጠር በሚያስቸግር መልክ ያከማቻቸው ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችና ፈንጂዎች፣ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መሽኮልኮሊያዎችና በዋሻ ውስጥ ያሰራቸው ቤቶችና መዝናኛዎችም ጭምር ናቸው። አስተሳሰቡና ድርጊቱ በሙሉ የደረጃ እንጂ ከጀርመኑ የናዚዎች አስተሳሰብና ድርጊት የሚተናነስ አይደለም።

ሰሞኑን ደግሞ ወንድማችን አቶ ኦባንግ ሜቶ የጥቁርና የነጭ ጁንታዎች የሚል ስም በመስጠት የወያኔን ድርጊት ብቻ ሳይሆን እስካሁን ድረስ አቅፈው ደግፈው ይረዱትና ግፋበት እያሉ ከጎኑ ቆመው የነበሩትን የነጭ ጁንታዎችም ፖለቲካ በጥልቀት እንድንመረምረው አስገድዶናል። ይሁንና የጥቁሩ ጁንታ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መደምሰሱ ወደ ፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደትና በዲሞክራሲያዊ አገር ግንባታ ላይ የቱን ያህል አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኑረው አይኑረው ከአሁኑ መገመት በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ የአገራችንን ፖለቲካ፣ የኃይል አሰላለፍና በፖለቲካው ውስጥ የተሳተፉትን ኃይሎች ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ብሄራዊ ንቃተ-ህሊና እንድንመረምር አስገድዶናል። የእኛ ጥያቄ ይህ ዐይነቱ ፋሺስታዊ አስተሳሰብና አረመኔያው ተግባር የክርስቲያኖችና የእስላሞች አገር ተብላ በምትታወቀውና፣ ልዩ ዩ ባህሎች ባሏት አገር ውስጥ እንዴት ሊከሰት ቻለ? የሚለው ነው። ይህ ዐይነቱ አገርን በአመረረ መንፈስ ለማፈራረስ መነሳትና ህዝባችን ለዝንተ-ዓለም እርስ በርሱ እየተበላላ እንዲኖር ለማድረግ ማቀድ ከየት የመጣ አስተሳሰብ ነው? አንድ ሰው ወይም አንድ ቡድን በተወለደበት፣ በአደገበትና ትምህርትቤት ሄዶ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ለቁም ነገር በደረሰበት አገር እንዴት እንደዚህ አድርጎ ሊያስብ ይችላል? አገሩንና ባህሉን ለመጥላት የሚያስገድደው ነገር ምንድነው?  በፍልስፍናም ሆነ በስነ-ልቦና ሳይንስ በቀላሉ ሊገለጽ የማይችል አስተሳሰብና ድርጊት ነው። እነ ሂትለርም ሲነሱ አገራችንን ትልቅ እናደርጋታለን፣ „ከሁሉም የበለጥን ነን፣ ደማችንም ንጹህ ነው“ ብለው ተነሱ እንጂ፣ ጀርመንን ከዓለም ካርታ ላይ እንሰርዛታለን ብለው በፍጹም አልተነሱም። ይህ ማለት ግን የእነ ሂትለር አስተሳሰብ ትክክል ነው ማለት አይደለም።

በሁላችንም ዘንድ እስካሁን ድረስ መልስ ያላገኘውና ጥራትም የጎደለው የፖለቲካ ሂደት ትልቅ ውዥንብር ውስጥ ከቶናል። ወያኔን በሚመለከት በሁላችንም ዘንድ በከፊል ስምምነት ቢኖረንም፣ በሌላ ወገን ግን የወያኔን ስልጣን ላይ መውጣት በሚመለከትና 27 ዓመት ያህል ስልጣን ጨብጦ ተግባራዊ ያደረጋቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን በሚመለከት በመሀከላችን ምንም ዐይነት ስምምነት የለም። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ያለው ግንዛቤ፣ ህወሃት ወይም ወያኔ ከስልጣን  እስከተባረረበት ጊዜ ድረስ ተግባራዊ ያደረጋቸው ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች በሙሉ በራሱ መንፈስና ዕውቀት እየታገዘ እንጂ የውጭ ኃይል ወይም ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት የለበትም የሚል ነው። ይህ ዐይነቱ ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከፖለቲካ ሳይንስ የራቀ አባባልና አጻጻፍ አብዛኛዎቻችንን ግራ ያጋባ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት ለምናደርገው ዲሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ የአገር ግንባታ ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የጦርነት ሂደት ውስጥ የነበረውና ያለው ጣልቃ-ገብነት ግልጽ እስካልሆነልን ድረስ እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለጠንካራና ከድህነት ለሚያላቅቀው የኢኮኖሚ ግንባታ ያደረገው ያልተቋረጠ ትግል መና ሆኖ እንደሚቀር ካሁኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ሰሞኑን በደንብ ተከታትለን እንደሆን፣ ወንድማችን አቶ ኦባንግ ሜቶ ያነሳው በሁላችንም ዘንድ ይህን ያህልም ግንዛቤ ያላገኘው የተናገረውና ሀተታ የሰጠው ቁም ነገር አለ። አቶ ኦባንግ ያነሳው ነገር አዲስ ባይሆንም ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ባለፉት 20 ዓመታት ሳይታክተኝ በሎጂክ መልክ ለማስረዳት ብሞክርም፣ በተለይም ካለእኔ በስተቀር ፖለቲከኛ የለም እያለ እዚህና እዚያ ወጣቱን የሚያሳስተውን ምሁር ነኝ ባይ ለማሳመን ብሞክርም አሻፈረኝ በማለት አሁንም ቢሆን ወጣቱን በማሳሳት ላይ ይገኛል። ስለአገራችን ጉዳይና አልፎ አልፎም ስለ አንዳንድ አፍሪካ አገሮች የሚጽፈው ኢትዮጵያዊ አብዛኛውን ጊዜ አቀራረቡ ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የሚጻፍ ስላልሆነ፣ በተለይም ታዳጊውን ትውልድ የማሳሳት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። በስልት፣ በመመሪያ፣ በአንዳች ፍልስፍናና ርዕይ ላይ በመመስረት የሚጻፍ ጽሁፍ ባለመሆኑ በአንድ ህብረተሰብም ሆነ አገር ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና የስነ-ልቦና ቀውሶችን መነሻቸውን ወይም ምክንያቶቻቸውን ለመረዳት በጣም ያስቸግራል። ስለሆነም ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ደግሞ ሰለ ሪጅናል ቀውሶች የሚጽፉ ምሁራንን ጽህፎች ስናነብ መመሪያቸውንም ሆነ ርዕያቸውን ለመረዳት ከፍተኛ ችግር አለ። ይህ ዐይነቱ መመሪያና ርዕየ-አልባ አቀራረብ እየተለመደ በመምጣቱ በሁላችንም ዘንድ ሲንጸባረቅ ይታያል። በሌላ አነጋገር፣ በአብዛኛዎቻችን የሚቀርቡት ጽሁፎችና አነጋገሮች፣ ከሳይንስ፣ ከፍልስፍናና ከሶስዮሎጂ ውጭ የሆኑ አቀራረቦች በመሆናቸው በአገራችን ምድር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታና የፖለቲካ ስልጣንን ጨብጠውም አንዳችም መመሪያ ሳይኖራቸው በአቦ-ሰጡኝ ተግባራዊ የሚያደርጉትን ፖሊሲ ነክ ነገሮች ለመረዳት የሚያስችሉን አይደሉም ማለት ይቻላል።

ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ስንመጣ፣ በእኛ በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ ያለው የግንዛቤ ችግር፣ በተለይም ህወሃት የሚባለው ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ ድርጅት ወይም ቡድን እንዴት ስልጣን ላይ ለመውጣት እንደቻለና፣ በምንስ ተዓምር 27 ዓመት ያህል እንደዚህ ዐይነቱን የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ በመከተል መቋጠሪያ የሌለው የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ሊከተን ቻለ? በሚለው ላይ ምንም ዐይነት ስምምነትና ግንዛቤ የለንም። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት 27 ዓመት ያህል በአገራችን ምድር የተካሄደው ምንም ዐይነት የርዕይና የመመሪያ መሰረት የሌለው ፖለቲካ በሌላ ኃይል የተጠነሰሰ፣ የታለመና የታቀደ ሳይሆን በራሱ በህውሃት ብቻ ነው የሚል ነው። ስለሆነም፣ በአገራችን ምድር የተፈጠረው ቀውስ ሁሉ በሌላ ኃይል ሳይሆን በራሱ በህውሃት ብቻ የሚሳበብና፣ እሱም ከተወገደ በኋላ ሁሉም ነገር ሊስተካከል እንደሚችል ወደድንም ጠላንም መደምደሚያ ላይ የደረስን ጥቂቶች አይደለንም። በሌላ አነጋገር፣ ህወሃት የሚባለው ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣና ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ ከተውጣጡ ብሄረሰቤን እወክላለሁ ከሚሉት ጋር የጌታና የሎሌ ግኑኝነት በመፍጠር ያካሄደው ፖለቲካዊ የክፋፍለህ ግዛው ተግባርና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የውጭው ኃይል እጅ የለበትም የሚል ነው። በተለይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን የጎሳ ፌዴራሊዝምን ለተመለከተ የየክልሉ „አስተዳዳሪዎች“ የዋር ሎርድ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። እነዚህ ኃይሎች ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ዝቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ለውጭ ገበያ የሚሆን የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ከማስፋፋት በስተቀር በሚያስተዳድሩበት ክልል በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተና ሰፋ ያለ ህብረተሰብአዊ ሀብትን የሚፈጥር የኢንዱስትሪ ተከላ ባለማድረጋቸው በተለይም ለወጣቱ የስራ መስክ ለመክፈት የቻሉ አይደሉም። አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም ባህል በማዳበራቸውም አብጠውና ፈርጥመው በመውጣት የሚያስፈሩና ጭቋኞች ለመሆን በቅተዋል። ምንም ዐይነት የሞራልና የስነ-ምግባር ብቃትነት የሌላቸው ብሄረሰቤን እወክላለሁ በማለት ከህውሃት ጋር ያበሩት የየክልሉ „አስተዳዳሪዎች“ ዛሬ እንደምናየው በቤኔሻጉልና በኦሮምያ ክልል አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠር እዚያው ተወልዶና አድጎ፣ እንዲሁም ሀብት አፍርቶና የስራ-መስክ ከፍቶ የሚኖረው መጤ በመባል እንዲገደልና እንዲባረር ለመደረግ በቅቷል። በቀላሉ እልባት የማይገኝለት ይህ ዐይነቱ ክልላዊ አውቃቀር በውጭ ኃይሎች የታቀደ ለመሆኑ የታወቀና ለብዙ ዓመታትም ሲያወዛግበን የሚኖር ነው። የሃማኖት ሰዎች ነን የሚሉና ሰብአዊ መስለው፣ እንዲሁም በተራድዖ ስም ከምዕራብ አውሮፓና ከአሜሪካ የመጡና እንደልባቸው በጌትነት መንፈስ በአገሪቱ ውስጥ እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱና „የሚሰሩ“ ኃይሎች ዋናው ተግባራቸው የጥላቻን መንፈስ ማስፋፋት ነበር፤ አሁንም ነው። በሚንቀሳቀሱበት ወይም ደግሞ „ለስራ በተስማሩበት“ አካባቢ አዲስ ዐይነት የስራ ባህል፣ የስራ-ክፍፍልና ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትን  የሚያዳብር ስራ ሲሰሩና ሲያስተምሩ አይታይም። ሆን ብለው የያዙት በተለይም „አማራው እናንተን ይንቃችኋል፣ እንደሰው አያያችሁም“ እያሉ ያስፋፉት የነበረውና አሁንም የሚያስፋፉት የእንግሊዝና የሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገር ሰላዮች ዘር-ተኮር ለሆነው ጭፍጨፋ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉ አይደሉም። እነሱን መቆጣጠርና በአስቸኳይም ከአገር እንዲባረሩ ማድረግ የመንግስት ግዴታ ነው።

ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሆነና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በደንብ እንዳናነብ ያደረገን አጻጻፍና አባባል በአገራችን ምድር ብቻ ሳይሆን በአብዛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በፖለቲካ ስም የሚካሄደውን ዘረፋና በህዝቦች ላይ የሚወርደውን ግፍ እንዳንረዳ አዕምሮአችንን ጨፍኖታል ማለት ይቻላል። የግሪክ ፈላስፋዎች „አዕምሮ ማየት ካልቻለ ዐይንም ማየት አይችልም“ እንደሚሉት አባባል በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን ማየት ተስኖን የተሳሳተ ሀተታ እንድንሰጥ ለመገደድ በቅተናል፤ በዚህ ዐይነቱ ድርጊታችንም ከተጠያቂነት ልናልፍ አንችልም።

ይህንን የተዛባ፣ ከሳይንስና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ውጭ የሆነን አመለካከትና አቀራረብ የግዴታ መዋጋት ያስፈልጋል። ለምንስ ነገሮችን በተናጠል መመልከት እንደቻልንና፣ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማንበብ እንደተሳነንና የተሳሳተ ሀተታ እንደምንሰጥ እንደተሳነን ለማሳየት እሞክራለሁ። በተለይም ለአገሬና ለህብረተሰቤ ያገባኛል የሚልና አልፎም አልፎም የሚጽፍ ሰው ሳይንሳዊ ግንዛቤ እስከሌለው ድረስ የአገራችንን ችግር ከማባባስ በስተቀር ተግባራዊ መፍትሄ ለመስጠት በፍጹም አይችልም። አነሰም በዛም ዛሬ የበለጸጉና ጊዜያዊ ሰላም የሰፈነባቸውን አገሮች ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ የምንገነዘበው ሀቅ በጊዜው የተነሱት ምሁራን የየአገሮቻቸውን ችግሮች በትክክለኛው መነጽር ማየትና ማንበብ ባይችሉ ኖሮ ችግሩን ሊረዱና ከዚያም በኋላ መፍትሄ ለመስጠት ባልቻሉ ነበር። ስለሆነም የአገራችን ህዝብ ሰላም ያስፈልገዋል፣ አገራችንም ከውጥረት ተላቃ ህዝባችን ኃይሉን አስተባብሮ በአንድነት በመነሳት አገሩን እንዲገነባ ከተፈለገ የግዴታ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መመሪያ ያስፈልጋዋል የሚል ዕምነት አለኝ። አንድን ነገር በትክክለኛ መነጽር ማየት ካልተቻለና በቲዎሪ ደረጃ ሀተታ ለመስጠት ሙከራ እስካልተደረገ ድረስ ዛሬ በጉልህ የሚታየው ችግር እየባሰና እየተወሳሰበ በመሄድ ሁለትና ሶት ትውልድንም ትልቅ ችግር ውስጥ እንደሚከተው ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ያለን አማራጭ ሁለት ነው። አይ ነገሮችን ከሳይንስ አንፃር መመርመር፣ አሊያም ደግሞ እንደተለመደው በፊዩዳላዊ አቀራረብ አደባብሶ ማለፍ።

          የአገራችንን ሁኔታ በትክክለኛው መነፅር ማየት ያለመቻል ያስከተለው ችግር !

የተፈጥሮ ህግ ሆኖ በማንኛውም አገር ሰዎች ይኖራሉ። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም በተለያዩ ድሮች የተሳሰረን ማህበረሰብ ይመሰርታሉ። እነዚህም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ናቸው። እንደመንግስቱ አወቃቀርና የመንግስቱን መኪና በሚቆጣጠረው አገዛዝ የንቃተ-ህሊና ማነስም ሆነ መዳበር በዚያው ላይ መቅረትና የድህነት ሰለባ መሆን፣ አሊያም ደግሞ በማሰብ ኃይል በመታገዝ የተቀላጠፉ ተቋማትን መገንባትና፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ህብረተሰብአዊ ሀብትን ማዳበርና ግለሰብአዊ ነፃነትን መጎናፀፍ ይችላሉ። በአንድ አገር ውስጥ ከሁለ-ገብ ዕድገት ይልቅ ኋላቀርነት፣ ከግለሰብአዊ ነፃነት ይልቅ ሃሳብን በነፃ መግለጽ የማይቻል ከሆነ ይህንን ጉዳይ በህብረተሰብ ሳይንስና በፍልስፍና መነፅር እየታገዙ መመርመሩ የምሁራን ሚና ነው። ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ህብረተሰብ መሻሻልና ማደግ፣ እንዲሁም ደግሞ የተሟላ ኑሮና ነፃነት ስለሚያስፈልገውና ስለሚሻም፣ ከመሻሻልና ነፃነትን ከማግኘት ይልቅ ዕጣው ድህነትና መቋጠሪያ የሌለው ጦርነት ውስጥ የሚዘፍቅ ከሆነ ለዚህ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች የግዴታ መመርመርና መልስም ለማግኘት መሞከር በተለይም የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል ሞራላዊ ግዴታ ነው። እንደዚህ ከማድረግ ይልቅ ዝም ብሎ የሚመለከት ምሁር ወይንም ደግሞ የተሳሳተ ሳይንሳዊ የሚመስል ግን ደግሞ ከዕውነተኛው ሳይንሳዊ አተናተን ዘዴ የሚርቅ ገለጻ ወይም ሀተታ የሚስጥ ከሆነ ችግሩ እየተባባሰ ከሄደና አገሩም ከውስጥም ሆነ ከውጭ በመወጠርና ወደ ጦርነት እንድታመራ የምተደረግ ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም።

በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሰፈነን ሆነ የተዋቀረን አገዛዝ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰብአዊ ግኑኝነቶች ለመመርመር የሚያስችሉ ዘዴዎች ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እንደየጊዜው የኃይል አሰላለፍና ንቃተ-ህሊና በመነሳት ፈልቀዋል። በተለይም ፍስልፍና የአንድን አገር የገዢ መደብ ባህርይ መመርመሪያ መሳሪያ ሆኖ መወሰድ ከጀመረ ከሶስት ሺህ ዐመት ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተለመደ አንድን ህብረተሰብና የአገዛዙን ባህርይ መመርመሪያ ዘዴ አለ። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ ከምህታዊ (Mythology) ወይም በዘልማዳዊና ሎጂካዊ ባልሆነ የአነጋገር ዘዴና አስተሳሰብ ተላቆ አንድን ነገር በአርቆ-ማሰብ ወይም በሎጂካዊ መነፅር ማየትና መመርመር ከጀመረ ወዲህ በተለይም በአውርፓ ምድር ውስጥ በጭፍንና የሆነውን ያልሆነውን በማውራትና በመዘባረቅ ወደፊት መራመድ እንደባህል ሆኖ መወሰድ አልተለመደም። በመሆኑም የካፒታሊዝምን ዕድገት በምንመረምርበት ጊዜ ካፒታሊዝም ታቅዶና ታስቦ የተደረሰበት ማህበረሰብ ባይሆንም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገትና፣ ከተማዎችና መንደሮች በስነ-ስርዓት መገንባት የአርቆ-ማሰብና የሎጂክ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ካፒታሊዝም ከማደጉ በፊት ለዕድገት ማነቆ የሆነቱንና በየጊዜው ለጦርነት መነሺያና የእርስ በርስ መተላለቅ ዋናውን ምክንያት ማጥኛ ዘዴ ፍልስፍና ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ፣ ሌሎች ዕውቀቶች ማለትም የፖለቲካ ቲዎሪና ሶስዮሎጂ የህብረተሰብን ችግር መመርመሪያ ሆነው መዳበር እስከቻሉበት እስከ 18ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፍልስፍና ዋናው የመመርመሪያ መሳሪያ ዘዴ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በሌላ ወገን ግን፣ ፍስልፍናዊ አመለካከት በራሱ በሁለት የተከፈለ በመሆኑ በፈላስፋዎች ዘንድ የአንድን ህብረተሰብ ችግርም ሆነ የዕውቀት ምንጭን ለመመርመር ስምምነት አልነበረም። የመጀመሪያው ማንኛውንም ነገር፣ የተፈጥሮን አወቃቀርም ሆነ የህብረተሰብን ሁኔታ በአርቆ-ማሰብ ኃይልና በጭንቅላት ውስጥ በማብላላት ችግሩን ማግኘትና ዕውቀትንም ማዳበር ይቻላል ተብሎ ሲታመን፣ ይህንን የማይቀበለው ደግሞ የዕውቀት ዋናው ምንጭ በቀጥታ ከምናያቸው የሚፈልቁ ናቸው ብሎ የሚያምን ነው።  ይህ ዐይነቱ ነገሮችን ነጣጥሎ በማየትና በተለይም አንዳንድ ተጨባጭ የሚመስሉ(Facts) ነገሮችን በመውሰድ ጥናት የሚጠናበትና እንደማስረጃም የሚወሰድ ዘዴ ኤምፕሪሲዝም ተብሎ ይጠራል። ይህ ዐይነቱ ተቀባይነትን ያገኛና በየአገሮች ውስጥ „እንደመማሪያና መመርመሪያ ዘዴ“ ሆኖ የተወሰደው በተወሰኑ ነገሮች ላይ (Facts) የተመሰረተ የመመርመሪያ ዘዴ በአሽናፊነት በመውጣት ቀደም ብሎ በሶክራተስና በፕላቶ፣ በኋላ ደግሞ እንደ ላይብይኒዝና ካንት በመሳሰሉት፣ እንዲሁም በሌሎች በታወቁ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች የተደረሰበትን ተፈጥሮንም ሆነ የህብረተሰብን ሁኔታና ህግ መመርመሪያ ዘዴ በመቅበርና በአሸናፊነት በመውጣት በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን እንዳናይ ተገደናል። በተለይም እንደኛ ባለው ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ጥናትና ክርክር ባልተለመደበት አገር ይህ ዐይነቱ ሶፊስታዊ ወይም ኢምፕሪሲስታዊ አመለካከትና አተናተን እንደዋናና ትክክልኛ መረጃ መሰብሰብያ ዘዴ ሆኖ በመወሰዱ በአገራችን ምድር፣ በፖለቲካ፣ በማህበረሰብ፣ በኢኮኖሚው፣ በባህልና በስነ-ልቦና…ወዘተ. ያለውን የተዘበራረቀና የተዝረከረከ ሁኔታ፣ እንዲሁም ደግሞ ካለዕውቀት ወይም ሳይንሳዊ-አልባ በሆነ መንገድ በገዢዎችና በፖሊሲ አርቃቂዎች ተግባራዊ የሚሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመረዳት እንዳንችልና ሳይንሳዊ ትንተናም እንዳንሰጥ ተገደናል።

ከዚህ ዐይነቱ አጭር አገላለጽ ስንነሳ በአለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ምድር የተፈጠሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ልቦናና የባህል ቀውሶች፣ እንዲሁም ደግሞ በጎሳ ስም ተሳቦ የሚካሄደው ጦርነትና፣ በተለይም ዛሬ በከፋ መልክ በአንድ ብሄረሰብ ላይ ያነጣጠረ ለመስማት የሚዘገንን ድርጊት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ምክንያቶቹስ ምንድን ናቸው? እነዚህ ቀውሶች ከራሳችን የማሰብ ድክመት የፈለቁ? ወይስ ከውጭ ሰተት ብሎ ከገባው በተለያየ መልክ የሚገለጽ ተፅዕኖና ርዕዮተ-ዓለም ጋር የተያያዙ? በተለይም በአገራችን ምድር የሚካሄደው ጦርነት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት አለበት ወይ? ወይስ የለበትም? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ስናነሳና መልስም ለመፈለግ ስንቃጣና እርስ በርሳችን ስንከራከር ብቻ ነው አንዳች መቋጠሪያ የሚገኝለት መፍትሄ ማግኘት የምንችለው። በሌላ ወገን ግን በተለይም ያለፉትን 27 ዓመታት በተለያዩ ምሁራንም ሆነ በአንዳንድ ጸሀፊዎች ብዙም ሳይታሰብና ዘዴ (Method) ሳይኖረው የሚቀርበውን ሀተታ የሚመስል አቀራረብ ለተመለከተ፣ 1ኛ) ከውስጥ መሰረታዊ ምክንያቶችን ለማወቅና ለመርመር ሙከራ አይደረግም። አብዛኛዎች አቀራረቦች ኢ-ሳይንሳዊና፣ ይህን ያህልም በጭንቅላት ሳይብላሉ ዝምብለው የሚጻፉ ናቸው ማለት ይቻላል። 2ኛ) አብዛኛዎቹ ተንታኞች በአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የትርምስ ሁኔታ ወስጥ የውጭ ኃይሎች እጃቸው የለበትም። የእኛን አገር መፈረካከስ ወይም በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ መገኘት ፍላጎታቸው አይደለም የሚል በጣም የየዋሆች አቀራረብ አለ። ስለሆነም ይሉናል እንደዚህ ዐይነት ተንታኞች፣ የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም እንደ አሜሪካንና እንግሊዝ የመሳሰሉት ከፍተኛ የሞራልና የስነ-ምግባር ብቃትነት ስላላቸውና በአፈጣጠራቸውም ሰብአዊ ስለሆኑ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሰለች የተባረከችንና የተቀደሰችን አገር በአንድነቷ ጸንታና በኢኮኖሚ አድጋ ለማየት ይፈልጋሉ፣ ምኞታቸውም ነው ይሉናል። 3ኛ) ከዚህ ስንነሳ በተለይም ስልጣንን በጨበጠው ኃይልና በውጭ ኃይሎች መሀከል የጥቅም መተሳሰርና የእከክልኝ ልከክልህ ዐይነት ፖለቲካአን አንድን አገርና ህዝብ የማተረማመስ በፖለቲካ ስም የሚካሄድ ውንብድና በፍጹም የለም። በአገራችን ምድር የተፈጸሙት ወንጀሎች፣ ምዝበራዎችና አንድን ህዝብ ደሀና አቅመ-ቢስ አድርጎ ማስቀረት በአገዛዙ ወይም ኢትዮጵያን በተለያዩ ጊዜያት ሲገዙ በነበሩ ሰዎች ብቻ የሚሳበብ፣ ወይም ደግሞ ተጠያቂዎቹ እነሱ ብቻ ናቸው ወደሚለው ድምደማ ላይ ይወስደናል። አዲስ ሳይንስና ልዩ ዐይነት የአተናተን ዘዴ ተማርን ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብና አመለካከት ለምን የተሳሳሰተና አደገኛም እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ። በእኔ ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ የሰላም መስፈን፣ ግለሰባዊም ሆነ ህዝባዊ ነፃነትና ዲሞክራሲ ሊያብቡና አንድ አገርም ቀስ በቀስ ግን ደግሞ ወደ ተስተካከለና ፍትሃዊነት ወዳለው ዕድገት ሊያመራ የሚችለው ምሁሩ በሚሰጠው ሳይንሳዊ ትንተናና የችግር መፍቻ ዘዴ ብቻ ነው። ሳይንሳዊ የአተናተን ዘዴ ባልተለመደበትና ክርክር በሚፈራበት አገር ሌላው ቀርቶ ቀላል ችግሮችን መረዳትና መፍትሄም መስጠት በፍጹም አይቻልም። ከዚህ ስንነሳ ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ጀምሮ በአገራችን ምድር ውስጥ የተፈጠሩት ቀውሶች በሙሉ ካፒታሊዝም በተኮላሸ መልክ ከገባበት ጊዜና ለሁለገብ ዕድገት የማያመች የትምህርትና አዲስ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምና የአመራረት ስልት በመከተላችንና፣ ከካፒታሊስቱ ዓለም ጋር በነበረንና ካለን፣ ይሁንና ደግሞ በራሳችን እንዳንተማመንና ጥገኛ እንድንሆን ካደረገን የጠበቀ ግኑኝነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ግሎባል ካፒታሊዝም ተብሎ የሚጠራው በተለያዩ ዐይነቶች የሚገለጸው፣ ማለትም በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በዕዳና በፋይናንስ ካፒታል፣ በዓለም አቀፋዊ የምርት ክንውንና፣ የአመራረት ክንውን መተሳሰር(Value-added chain)፣ ባልተስተካከለ ንግድና በብዝበዛ የሚገለጸውና በመንግስታትም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድረው የእንደኛ የመሰለውን አገር የመኖርና ያለመኖር ዕድል የሚወሰን ነው። ስለሆነም የዛሬው ካፒታሊዝም ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው ካፒታሊዝም ጋር ሲወዳደር በብዙ እጥፍ የሚለይና፣ በጣምም የተወሳሰበ ነው። አንድን ደካማ አገር የተወሳሰበ ወጥመድ ውስጥ በማስገባት እዚያው በዚያው እንዲንደፋደፍ የሚያደርጉ የተወሳሰቡና ለአብዛኛዎቻችን ግልጽ ያልሆኑ መሳሪያዎች አሉት። የዛሬው ኢምፔሪያሊዝም አንድን አገር በቁጥጥሩ ስር ለማድረግና ሀብቱን ለመዝረፍ የግዴታ የቀጥታ ወረራ ማካሄድ አያስፈልገውም። ስለሆነም የተለያዩ የብዝበዛ መሳሪያዎችን ያዳበረውና ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የሚቆጣጠረው የካፒታሊስቱ ዓለም የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮችን ዕድል ወሳኝ ነው። በጎሳና በሃይማኖት ስም ተሳበው በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው።

                አምባገነናዊ ወይም ፋሺስታዊ አገዛዝ የግዴታ የግሎባል ካፒታሊዝም ውጤት ነው!

አንዳንዶች ይህንን አርዕስት በሚያዩበት ጊዜ እንዴት ፋሺዝም ወይም አምባገነናዊ አገዛዝ ከካፒታሊዝም ጋር ሊያያዝ ይችላል? ለመሆኑ ካፒታሊዝም ወይም ግሎባል ካፒታሊዝም የሚባል ነገር አለ ወይ? ሊኖር የሚችለው፣ የምንኖርበትና የምንጠቀምበት ስርዓት ካፒታሊዝም ሳይሆን የገበያ ኢኮኖሚ አይደለም ወይ? እንደዚህ ብሎ መጻፍስ ከንጹህ ጥላቻ ወይም ለአንድ ርዕዮተ-ዓለም ካለ አፍቃሪነት በመነሳት አይደለም ወይ? ዓለምስ ወደ አንድ መንደር እያመራች አይደለም ወይ? ይኸው እንደምናየው ግሎባላይዜሽን የሚባለው ነገር ከተስፋፋ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ዕድገት እየታዩ አይደለም ወይ? ካፒታሊዝም ወይም ግሎባላይዜሽን እያሉ መጻፍ ወደ አረጀ አስተሳሰብ መመለስ አይደለም ወይ? እያሉ መዓት ጥያቄዎችን ሊያቀርቡ ይችላሉ። በእርግጥ ትችታዊ አመለካከት ባልዳበረበት፣ ህብረተሰብአዊ አወቃቀሮችን መመርመር ባልተለመደበት፣ ማንኛውም ስርዓት እንደክንውናዊ ሳይሆን እንዳለ ወይም በዚያው ቆሞ እንደሚቀርና ወደፊትም እንደሚኖር ተደርጎ በሚወሰድበትና፣ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መገንዘብና መተንተን ባልተለመደበት አገር እንደዚህ እያሉ መጻፉ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ሊከተን ይችላል ተብሎ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይችል ይሆናል።

በመጀመሪያ ደረጃ ጸሀፊው አምባገነናዊ ወይም ፋሺስታዊ ስርዓትን ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር አያይዞ ሲጽፍ ከንጹህ ጥላቻ ወይም ለሌላ ርዕዮተ-ዓለም ካለው ናፋቂነት በመነሳት ሳይሆን ከጥናትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ከመገንዘብና በትክክል ከማንበብ በመነሳት ነው። ስለ ካፒታሊዝም ወይም ስለ ግሎባል ካፒታሊዝም መጻፍና ትንታኔ መስጠት ያለፈለበት ጉዳይ ሳይሆን ዛሬም ቢሆን የሚጠናና ትንታና የሚሰጥበት ጉዳይ ነው። በምዕራቡ ዓለም በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ምርምር የሚደረግበተና እንደ ትምህርትም የሚሰጥ ነው። ተቀባይነት ካገኘው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ውጭ የሚመራመሩ ፕሮፌሰሮችም ሆነ ጠለቅ ያለ ምርምር የሚያደርጉ ጋዜጠኞች ስለ ካፒታሊዝም ወይም ስለግሎባላይዜሽን መጽሀፎችን በየጊዜው ይጽፋሉ፤ በጆርናሎችም ላይ በየጊዜው አዳዲስ ሀተታዎች ይቀርባሉ። ስለሆነም አርዕስቱ ያረጀ ሳይሆን እንዲያውም ጊዜያዊና በሚገባ መጠናት ያለበት ጉዳይ ነው።

እዚህ ላይ ስለ ካፒታሊዝም ምንነት ወይም እንደ ኢኮኖሚ ስርዓት ትንተና መስጠት አያስፈልግም። ይሁንና ለምን ካፒታሊዝም ወይም ግሎባላይዜሽን ለፋሺዝም ምንጭ ወይም መነሻ ምክንያት ሊሆን ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው።  በመጀመሪያ ደረጃ ቀደም ብለው ከነበሩት ስርዓቶች ጋር ሲወዳደር በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ወይም በካፒታሊዝም አማካይነት ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ምጥቀትና ሳይንሳዊ ግኝቶች ሊታዩና የሰው ልጅም ኑሮ ሊሻሻል ችሏል። በሳይንስ አማካይነት አዳዲስ መድሀኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች በመፈጠራቸው ባህላዊ በሆኑ መንገዶች ማዳን የማይቻሉ በሽታዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መፈወስ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪ አብዮት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ምጥቀት የተነሳ የሰውም አስተሳሰብ መዳበር ችሏል። በየጊዜው የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን በተለያየ መልክ መግለጽ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህም በላይ በቴክኖሎጂ ዕድገትና መስፋፋት የተነሳ የሰው ልጅ ተንቀሳቃሽና ከተወለደበት አገር ወጥቶ ሌላ አገር የሚኖርበት፣ የሚማርበትና የሚሰራበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። እንደ ሊበራሊዝምና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚባሉ አስተሳሰቦች ቀደም ብለው የተደረሰባቸው ጽንሰ-ሃሳቦች ቢሆኑም ተግባራዊ መሆን የጀመሩት በቴክኖሎጂ መዳበር የተነሳ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሲመጣና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲፈጠሩ ነው። ስለሆነም ጸሀፊው የካፒታሊዝምን ምንነትና አስተዋፅዖ የሚዘነጋ አይደለም፤ ጭፍን ጥላቻም የለውም። ይሁንና ግን አንድ ክሪቲካል አመለካከትያለው ሰው ማድረግ የሚገባውን የአንድን ስርዓተ ማህበር ውስጣዊ ቅራኔና በየጊዜው ብቅ የሚሉ አንድን ህብረተሰብ ሊያናጉም ሆነ ወደ ጦርነት ውስጥ ሊከቱት የሚችሉ ከአርቆ አሳቢነት ጉድለት የሚወሰዱ ፖሊሲዎችንና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎችን የመተንተንና የማሳየት ሞራላዊ ግዴታ አለበት።

ለማንኛውም ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው ብዙ ውጣ ውረዶችን ካሳለፈ በኋላ እንደሆነ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን የብዙ ውጣ ውረዶች ውጤት ነው። እንደ ሬናሳንስ፣ ሪፎርሜሽንና ኢንላይተንሜንት የሚባሉት ጭንቅላትን የሚያድሱና ብሩህ የሚያደርጉ አስተሳሰቦች ባይፈጠሩና ባይተገበሩ ኖሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልተፈጠሩ ነበር። በመንፈስ ተሃድሶ አማካይነት ብቻ ነው አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሊደረሰባቸውና ሳይንስና ቴክኖሎጂም ዕውን ሊሆኑ የቻሉት። ለሳይንስ ግኝትና ምርምር አንዳንድ የተገለጸላቸው ተመራማሪዎች ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ከለመዱት ኑሮና የአገዛዝ ስልት ላለመላቀቅ የፈለጉ የሃይማኖት መሪዎችና የአሪስቶክራሲው መደብ በሳይንቲስቶችና በፈላስፋዎች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ አካሂደዋል። አንዳንዶችም እስከነነፍሳቸው አቃጥለዋቸዋል። አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ የበቁም ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም።  የኋላ ኋላ ግን አዲስ የህብረተሰብ ክፍል እየተፈጠረና እየዳበረ ሲመጣ፣ እንዲሁም ደግሞ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የአመራረት ስልትና የንግድ ልውውጥ ሲዳብር አዳዲስ የህብረተሰብ ኃይሎች ብቅ ማለት ይጀምራሉ። ይህ ዐይነቱ የኃይል አሰላለፍና የህብረተሰብአዊ ለውጥ የግዴታ ይበልጥ ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በዚያው መጠንም ልዩ ልዩ ቲዎሪዎች ይፈልቃሉ። በምሁራን ዘንድ የጦፈ ክርክር ይደረጋል። እንደየሁኔታው ምሁሮችም ተጨባጭ ሁኔታዎችንና የኃይል አሰላለፎችን በተለያየ መነፅር መመልከትና መተንተን ይጀምራሉ። አንዳንዶቹ የኢንዱስትሪ አብዮትን ውስንነት በመገንዘብ ለሰብአዊነት፣ ተከታታይነት ለሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገትና፣ በተለይም ደግሞ የተፈጥሮን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ የሚያሰገባ ስርዓት መፈጠር አለበት ብለው ሲከራከሩ፣ ሌሎች ደግሞ አዲስ ለተፈጠረው የህብረተሰብ ኃይልና ቀስ በቀስ ኢኮኖሚውን ለሚቆጣጠረው ጠበቃ በመቆም የራሳቸውን ቲዎሪ መፍጠርና ማዳበር ይጀምራሉ። ይህ ሁኔታ የግዴታ ወደ ርዕዮተ-ዓለም ትግልና ክርክር ያመራል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የአመለካከት ወይም በርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ ትግል የተጀመረው በእነማርክስ ዘመን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ሳይሆን ቀደም ብሎ በ15ኛውና በ16ኛው ክፍለ-ዘመን የተጀመረ ለመሆኑ አያሌ ምርምሮችና ጥናቶች ያረጋግጣሉ፤ በመጽሀፍም ተመዝግበዋል። አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ ወደ ኋላ በመሄድ ይህ ዐይነቱ በግሪክ የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የነበረና፣ በተለይም በአንድ በኩል በሶክራተስና ፕላቶ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሶፊስቶች መሀከል የአመለካከት ወይም ተፈጥሮንና የህብረተሰብን ግኑኝነት በማንበብ ረገድ የጦፈ ክርክር ይካሄድ እንደነበር ያመለክታሉ። የኋላ ኋላ ደግሞ በስቶይኮችና በኢፒኩሪያን መሀከል እንደዚሁ፣ መንፈሳዊንና የማቴሪያላዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የጦፈ ክርክር ይካሄድ እንደነበር የሚያመለክቱ አያሌ ጥናቶች አሉ። ከዚህም በመነሳት ከማቴሪያላዊ ኑሮ ይልቅ መንፈሳዊ አስተሳሰብን ማስቀደምና ማንኛውም ሰው ሞራል እንዲኖረው ይገባል በሚለውና፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሰው ልጅ ጥቅሙን ማስቀደም አለበት፣ በአፈጣጠሩም ስግብግብ ስለሆነ ይህ ዐይነቱ ስግብግብነት የግዴታ ለማቴሪያላዊ ዕድገት ያመቻል በሚሉት መሀከል የአሰተሳሰብ ውድድር ይታይ ነበር። ማቴሪያላዊ ዕድገትን፣ ለራስ ጥቅም መቆምንና ጥቅምን ማሳደድ የሚሉት አስተሳሰቦች የኋላ ኋላ በአሸናፊነት በመውጣት የካፒታሊዝም ስርዓት ወይም የገበያ ኢኮኖሚ ተብሎ ለሚጠራው መለዮ ሊሆኑ ችለዋል። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ በተለይም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቶችን ጭንቅላት ሊቆጣጠር ችሏል። ይህንን በሚመለከት ቶማስ ሲድላሴክ(Tomáš Sedláček) የሚባለው የቼክ ዜግነት ያለው ኢኮኖሚስትና የባንክ ሰራተኛ ጥሩውና ሰይጣናዊ ኢኮኖሚ(Economics of Good and Evil) በሚለው በጣም ግሩም መጽሀፉ በዚህና በሞራል ጉዳይ ዙሪያ ከሶስት ሺህ ዓመት ጀምሮ ወይም ቀደም ብሎ ከፍተኛ ክርክርና ትግል ይካሄድ እንደነበር ያመለክታል። መጽሀፉም የተጻፈው በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ሳይሆን እ.አ.አ በ2009 ዓ.ም ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነው ማለት ነው። ስለሆነም ካፒታሊዝም ወይም ግሎባል ካፒታሊዝም፣ ወይም ደግሞ ኢምፔሪያሊዝም እያሉ መጻፍ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ወይም የአክራሪዎች አስተሳሰብ ሳይሆን የተረማጅነትና የተገለጸለት አስተሳሰብ ነው።

ከዚህ ስንነሳ እኛ ምሁራን ተብለን በምንጠራው መሀከል ያለው ትልቁ ችግር የዓለምን ሁኔታ በጥቁርና በነጭ እየከፋፈሉ ማየቱ ላይ ነው። በተለይም ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩት ቀውሶች፣ በሶስተኛው ዓለም የሰፈኑት አምባገነናዊ ወይም ፋሺስት መሰል አገዛዞች የሚያያዙት ከኩሙኒዝም ጋር እንጂ ከካፒታሊዝም ጋር አይደለም። ኮሙኒዝም በአፈጣጠሩ ግለሰብአዊ ነፃነትን ገፋፊ፣ የመደብለ ፓርቲ ተቀናቃኝና ብዙሃዊነትን የማይፈቅድ በመሆኑ ይህ ዐይነቱ ርዕዮተ-ዓለም የግዴታ አምባገነናዊ አገዛዝን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስፋፋና የሚያስፈፋ ነው የሚሉ ብዙ ምሁራኖች አሉ። በሌላ ወገን ግን ካፒታሊዝም በስምምነትና በፈቃድ፣ እንዲሁም ግለሰብአዊ ነፃነትን በማክበር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በአንዳች መንገድ ወደ ሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ውስጥ በሚስፋፋበት ጊዜ የግዴታ ግለሰብአዊ ነፃነት እንዲኖር፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብና፣ በተለይም ደግሞ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩት ተጠያቂነት የሚሰማቸውና የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ስርዓት በመሆኑ ለዕድገት አጋዥ ነው ይሉናል። ይህ ዐይነቱ በአንድ በኩል ኮሙኒዝምን እንደጭራቅ መሳልና ማየት፣ በሌላ ወገን ደግሞ ካፒታሊዝምን መልአኮችና ቅዱሳኖች የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት ስርዓት እንደመሆኑ መጠን ስልጣንን የሚቆጣጠሩትና ኢኮኖሚውን የሚያሽከረክሩት ኃይሎች በሙሉ ዋና ዓላማቸውና ድርጊታቸው ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ማስፈንና የተስተካከለ ዕድገትን ማምጣት ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ለተስተካከለና ፍትሃዊነት ላለው ዕድገትና ለብሄራዊ ነፃነታችን እንቅፋት ለመሆን ችሏል። ስለሆነም ጦርነትም ሆነ አምባገነናዊ ስርዓት ከካፒታሊዝም ጋር የሚያያዙ ሳይሆን አንድ ወጥ ከሆነው ከኮሙኒስታዊ አገዛዝ ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው የሚል አዲስ ዐይነት የፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና ያስተምሩናል።

ሀቁ ግን በመጀመሪያ ደረጃ ካፒታሊዝም ተፈልጎ፣ ታቅዶና በስምምነት የተገነባ ስርዓት ሳይሆን የብዙ አጋጣሚዎች ውጤትና ከብዙ ማህበረሰብአዊ ክንውኖችና ከውጭ በመጣ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ተጽዕኖና፣ ይህንን ውስጣዊ (Internalize) በማድረግ፣ በማስፋፋትና በማዳበር በአጋጣሚ እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ የተደረሰበት ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ቅንጅት ነው። ይህም ማለት፣ ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ማቲማቲክስ ከውጭ ቢመጡም በተገለጸላቸውና በገባቸው ምሁሮች አማካይነት እነዚህ ዕውቀቶች ሊዳብሩና ለሁለ-ገብ ዕድገት ሊውሉ ችለዋል። በሌላ አነጋገር፣ እነዚህ የተገለጸላቸው ምሁራን ህይወታቸውን ባይሰዉና ከአክራሪ የሃይማኖት መሪዎችና ከዲስፖታዊ አገዛዞች የሚመጣባቸውን ጫናና ጭቆና ባይቋቋሙና ታግተው ባይሰሩ ኖሮ የአውሮፓ ህብረተሰብ ልክ የእኛ ዐይነቱ አገር ዕጣ በደረሰበትና በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ በኖረ ነበር። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ጥናቶችና ምርምሮች ይህንን ዐይነቱን በአንዳንድ ግለሰቦች የተደረገን የጭንቅላት ትግልና የተለያዩ ሁኔታዎች በመገጣጠም ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን እንደፈጠሩ ነው የሚያረጋግጡት። ይሁንና ግን ካፒታሊዝም እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ በተለያዩ ምሁራን ዘንድ ዕድገትንና ዕውቀትን በሚመለከት የተለያየ ትርጓሜ በመሰጠት በተለይም ብቅ ብሎ ለወጣው አዲስ የገዢ መደብ የሚስማማ ትምህርት መቀረጽ ተጀመረ። ዕውቀትንም ከሰብአዊነትት ባህርይው በማላቀቅ መደባዊ ባህርይ እየያዘ መምጣት ቻለ። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት በሶሻል ሳይንስ፣ በተለይም ደግሞ በትምህርት ቤት በሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ላይ የሚንጸባረቅ ነው። የህብረተሰብን በተለይም የካፒታሊዝምን ዕድገት በደንብ ለመመርመርና እንዴትስ እንደሚሰራና እንደሚንቀሳቀስ እንዳንረዳ ወይም እንዳይገባን በረቀቀ (Abstract) መልክ ሊቀረጽ በመቻሉ፣ እንደነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ በመሳሰሉትና፣ በኤክስፐርት ስም በአማካሪነት በሚመጡትና ብዙ ሺህ ዶላር እየተከፈላቸው በሚያሳስቱን በቀላሉ ልንታለልና በአገራችን ምድር ድህነት እንዲስፋፋና ያለው ኋላ-ቀርነት ስር እንዲስድ ለማደረግ በቅተናል። የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስም ከታሪካዊ ሁኔታዎች፣ በተለይም የአውሮፓው ማህበረሰብ እንዴት አድርጎ ከፊዩዳሉ ስርዓትና ከትናንሽ የአመራረት ስልቶች ወደ ተወሳሰበና ወደ ካፒታሊስቱ የአመራረት ስልት ሊሸጋገር እንደቻለ በማገናዘብና ከሁሉም አቅጣጫ በማጥናት የሚሰጥ ባለመሆኑ፣ የካፒታሊዝምን ዕድገት ወደ ተራ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በተለይም ወደ ተራ ንግድ እንቅስቃሴ ለመቀነስ አስችሎታል። ባህላዊና የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የፖለቲካ ጥገናዊ-ለውጥ፣ የመንግስት መኪና ከጭቆና ባህርይው መላቀቅና፣ ልዩ ልዩ ለህዝብ ግልጋሎቶች የሚሰጡና የጥሬ-ሀብትንና የሰውን ኃይል ለማንቀሳቀስ የሚችሉ ተቋማትና(Institutions)፣ የእነዚህም ተቋማት ዲሞክራሲያዊ ባህርይ መያዝ፣ እንዲሁም ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመች ትምህርት ሳይስፋፋ …ወዘተ. …ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሳይለወጡና ሳይሻሻሉ ነው ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለው ነገር ተግባራዊ ሊሆን የቻለው የሚለውን ትረካ እንዳምን ተገድደናል።  ስለሆነም ካፒታሊዝም በውስጣዊ ቅራኔ የሚገለጽ የኢኮኖሚ ስርዓት ሳይሆን ዕድገቱ ተከታታይነት ያለውና ሀብትንም በእኩል ደረጃ ለአምራቹም ሆነ የምርት ኃይሎችን ለሚቆጣጠሩት የሚያከፋፍል የኢኮኖሚ ስርዓት ነው። ቅራኔ ወይም ደግሞ የኢኮኖሚ ቀውስ ከታየ ከውስጥ የሚፈልቅ ሳይሆን ከውጭ የሚመጣ ነው። ይሁንና ማርክስም ሆነ ኬይንስ በሂደት ውስጥ በተለያየ ጊዜያት የሚከሰቱት ቀውሶች የካፒታሊዝም ውስጣዊ ህጎች ናቸው። በተለይም በኬይንስ አመለካከትና ዕምነት ካፒታሊዝም በየጊዜው ከሚከሰተው ቀውስ ሌፈወስ የሚችለው እንደ አዳም ስሚዝ ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች እንደሚነግሩን በገበያ ኃይሎች አማካይነት ሳይሆን በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት መንግስት ጣልቃ የገባ እንደሆን ብቻ ነው።

ስለሆነም እንደዚህ ዐይነት ተቆንጽሎ፣ ከህብረተሰብ የታሪክ አወቃቀርና ከባህላዊ ለውጥ ተነጥሎ የገባ ትምህርትና ተግባራዊ የሆነው ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ የሚባል ነገር በተለይም ከእንደኛ አገር የፈለቁ ምሁራንን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳሳት በቅቷል። እንደሚታወቀው ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ የሚባለው ፊስካል ፖሊሲን ማዕከላዊ ያደረገ የኢኮኖሚክ ፖሊሲ በ1930 ዓ.ም በኬይንስ ከመፍለቁ በፊት አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና አሜሪካም ጭምር ወደ ውስጥ ያተኮረ በካፒታሊስት ሎጂክ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነበራቸው። ሳይንስና ቴክኖሎጂን አዳብረዋል። ከተማዎቻቸውም በኢንፍራስትራክቸር የተያያዙ ነበሩ። ወደ አገራችን የገባው የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሳያካትት ነው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲሰጥ የተደረገውና ብዙ ተማሪዎችንና ፖሊሲ አውጭዎችን ለማሳሳት የበቃው።

ከዚህም የተነሳ በአገራችን ምድርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከካፒታሊዝም ጋር የተያያዙ አምባገነናዊ ስርዓቶች ድህነት እንዲፈለፈልና፣ የአንድን አገር ህዝብ አቅመ-ቢስ እንዲሆን ማድረግ የቻሉት ካለበቂ ምክንያት አይደለም። ከፍተኛ የዕውቀት ክፍተት በመኖሩም በአብዛኛዎቹ ዘንድ ካፒታሊዝም መቼ እንደተመሰረተና ዓለም አቀፋዊ ባህርይም ለመውሰድ እንደቻለ የተመረመረና ግንዛቤ ያገኘ አይደለም። ስለሆነም በአብዛኛዎቻችን የሚታወቀው ካፒታሊዝምና የካፒታሊዝም የተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ሳይሆኑ፣ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ የሚለው ከህብረተሰብአዊ ለውጥና ከምሁራዊ እንቅስቃሴና ከጭንቅላት ምርምር ጋር ያልተያያዘው ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔና የንግድ ልውውጥ ናቸው። በዚህ መልክ ግንዛቤ ያገኘው ወደ ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ የተለወጠው የምርት፣ የንግድና የፍጆታ አጠቃቀም ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ባህርይ የለውም።  በመሆኑም ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ በመባል የሚታወቀው ትላንት የነበረ፣ ዛሬ ያለና ወደፊትም የሚኖር ስርዓት ነው። በአገራችንም ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰብአዊና የመንግስት አወቃቀርና አምባገነናዊ ስርዓት ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር የሚያያዙ ሳይሆኑ ከውስጥ በራሳቸው ኃይል እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱና፣ በተለይም መንግስታዊ መኪናውና እሱን የሚቆጣጠሩት ኃይሎች በራሳቸው ኃይል የሚንቀሳቀሱና ህብረተሰቡን እንደፈለጉ የሚበውዙ ናቸው የሚል ድምደማ ላይ ደርሰናል።

ተጨባጩ ሁኔታና የካፒታሊዝም ዕድገት ግን የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን ምንነት የሚፃረሩ ናቸው። ብዙ ነገሮች በመጣመር ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን ቢፈጥሩም ትርፍና ውድድር የካፒታሊዝም አንቀሳቃሽ ኃይሎች ናቸው። ስለሆነም በካፒታሊስት ስልተ ምርት ውስጥ የምርት ወይም የኢኮኖሚው ዕድገት ዋናው ዓላማ በመጀመሪያ ደረጃ ህዝባዊ ፍላጎትን ማሟላት ሳይሆን ማንኛውም የምርት ክንውን ከዋጋና ከጥቅም ወይም ደግሞ ከትርፍ አንፃር ነው የሚሰሉት። በካፒታሊዝም የአመራረት ሂደት ውስጥ ባህልን መጠበቅና መንከባከብ፣ ሞራል፣ ሃይማኖትና ልዩ ልዩ እሴቶችና እንዲሁም የኢኮሎጂ ወይም የተፈጥሮ ጉዳይ ስሌት ውስጥ የሚገቡ ሳይሆን ካፒታሊዝም እነዚህን እየደመሰሰ የሚሄድና አዳዲስ ቅራኔዎችን የሚፈጥር ነው። የሰው ልጅም ምንነት የሚለካው በሙሉ ከኢኮኖሚ ስሌት፣ ከገንዘብና ከትርፍ አንፃር ሲሆን፣ አስተሳሰቡ በዚህ ዙሪያ የሚሽከረከር መሆን አለበት። በመሆኑም ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ ስሌትና አስተሳሰብ በአብዛኛዎቻችን መንፈሰ ውስጥ ሊከተል በመቻሉ ከዚያ ወጣ ብለን እንዳናሳብ ተገደናል። ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋና ሌሎች የአመራረትና የፍጆታ አጠቃቀሞችን ሲያወድም በሰዎች የስነ-ልቦና አቀራረጽ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለሁላችን ግልጽ ለመሆን ያልቻለው ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔን ከሌሎች ህብረተሰብአዊ ድርጊቶችና ፍላጎቶች ነጥለን በማየታችን ነው። በሌላ አነጋገር፣ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ በተለይም ዕውቀት ባልተስፋፋባቸውና ነገሮችን በሚገባ ማውጣትና ማውረድ ባልተለመደበት እንደኛ ባለው አገር የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም ዕድገትን የሚያመጣ እንጂ ሌሎች ማህበራዊ ቅራኔዎችን ሊፈጥር አይችልም የሚል ግንዛቤና ዕምነት በሁላችንም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ስለሆነም በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ውስጥ የሚታዩት የስነ-ልቦናና የባህል ቀውሶች፣ የወንጀለኛና የቀማኛ መስፋፋት፣ ማፊያ ነክ ተግባሮች መዳበር ከካፒታሊዝም ወይም ከኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የሚያያዙ፣ ወይም ደግሞ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግኑኝነቶች የሚፈጥሯቸው ቀውሶች ሳይሆኑ ባልታወቀ ምክንያት የሰዎች አስተሳሰብ ስለሚበላሽ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚታዩ ማህበራዊ ሁኔታዎች(Social Conditions) የሰዎችን አስተሳሰብ በጥሩም ሆነ በመጥፎ መልክ አይቀርጹም ይሉናል። በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ቀደም ብለው ከነበሩት የአኗኗር ኖርሞችና ባህሎች፣ እንዲሁም ሞራልና ስነ-ምግባር ጋር ሲወዳደሩ በተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በነፃ ንግድ አማካይነት የተነሳ አዳዲስ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እነዚህን ጠጋ ብሎ የሚመረምሩ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ባለመኖሯቸው በግልጽ የሚታዩና አደገኛ የሆኑ ባህርይዎችና ድርጊቶች ዝም ብለው ይታለፋሉ። አሊያም በዘልማዳዊና በተራ አነጋገር የዛሬው ትውልድ የተባላሸና የአገሩን ባህል የሚንቅ ነው ይባላል።  ለምንድነው የዛሬው ሁኔታ ከሃምሳና ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲወዳደር ሊለይ የቻለው? ለምንስ የሞራል ውድቀት ይታያል? ለምንስ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩት ቀደም ብለው ከነበሩት ስርዓቶች ጋር ሲወዳደሩ አረመኒያዊና መንፈሰ-አላባ ሊሆኑ ቻሉ? ብሎ የቀደመውን ስርዓት አሁን ከምናየው ጋር ለማወዳደር የሚፈልግ በፍጹም የለም። ሁላችንም ዝም ብለን ነው የምንነዳው።

ከዚህ ስንነሳ በተለይም የካፒታሊዝም ዕድገትና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ከኢኮኖሚና ከፍጆታ አጠቃቀም አልፎ የሶስተኛው ዓለም አገሮችን የመንግስት መኪና አወቃቀርም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መቆጣጠር፣ በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብዝበዛን ማጠናከርና ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ ማድረግ፣ ማህበራዊና ባህላዊ የአኗኗር ዘዴዎች እንዲዘበራረቁ ማድረግ… ወዘተ. … ወዘተ.፣  እነዚህ ሁሉ ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው። ይህ ማለት ግን በተለይም በአለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት የተደረገውን ቴኮኖሎጂያዊ ግኝቶችና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ከመሳት ወይም ከመዘንጋት የተነሳ ለመስጠት የሚሞከር ሀተታ ሳይሆን፣ ይህ ዐይነቱ ቁጥጥር ሳይደረግበትና ሳይጠና የገባ የፍጆታ አጠቃቀምና በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ ያልተመሰረተ ወይም ያልተደገፈ የአመራረት ዘዴ የቱን ያህል እንደኛ የመሳሰሉ አገሮችን ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታ እንዳዘበራረቀውና፣ በቀላሉም ለማረም እንዳማይቻል ለማሳየት ብቻ ነው። ለማሳየት የምሞክረው የስርዓቱን ውስጣዊ ቅራኔና፣ በዚህ ዓይነቱ የቅራኔ ህግጋት የሚመራ እንደሆነ፣ በአንድ በኩል ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ዕምርታን ለመቀዳጀት የቻለ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትንና አምባገነናዊ ስርዓትን እንዲያም ሲል ጦርነትን የሚያስፋፋ የተወሳሰበና በረቀቀ መንገድ የሚከናውን ስርዓትና፣ እንደየሁኔታውና ግለሰቦች እንደፈለቀቡትና እንደ አደጉበት የቤተሰብና የአካባቢ ሁኔታ የሰዎችንም ባህርይ አመጸኛ በሆነ መልክ ሊቀርጽ የሚችል መሆኑን ለማመልከት ብቻ ነው። ይሁንና ግን የሳይንስና የማቲማቲክስ ተመራማሪዎችና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ፈርን የቀደዱ ታላላቅ ተመራማሪዎች በጊዜው ለመመስረት የፈለጉት ስርዓተ-ማህበር ወደዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ኑሮ ከማቃለል አልፎ መጨቆኛ፣ መቆጣጠሪያና ጦርነትን አፍላቂና ሰውን መግደያ መሳሪያ ሊሆን ይችላል ብለው እንዳላሰቡ መገመት ይቻላል። የተሳሳተ ዕውቀትንና ሊያስከትል የሚችለውን ዓለም አቀፋዊ አደጋና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል እንደነላይቢኒዝ የመሳሰሉት የሳይንስና የማቲማቲክስ፣ የቴክኖሎጂና የቲዎሎጂ አፍላቂዎችና ተመራማሪዎች የዛሬ ሶስት መቶ ዓመት ጽፈው ነበር። በተለይም ኤምፕሪሲዝም በመባል የሚታወቀው በእንግሊዝ አገር የዳበረው በክስተት ላይ የተመሰረተው ፍልስፍናዊ አመለካከት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ካገኛና ተግባራዊ ከሆነ በተሳሳተ ርዕዮተ-ዓለም የተነሳ የሰው ልጅ ዕጣ የግዴታ ጦርነትና ድህነት መስፋፋት ይሆናል ብለው ተናግረው ወይም ጽፈው እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። ዛሬ የምናየው ሁኔታ ይህንን የመረረ ሀቅ ነው።

ስለሆነም ኋላ-ቀር ከሆነ ማህበራዊ አወቃቀር ጋር በመያያዝ ካፒታሊዝም የጦርነትና የፋሺዝም ዋናው ምንጭ የሆነበት ዋናው ምክንያት ከዚህ በመነሳት ነው። ከዚህም በላይ በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የፈለቀውና የዳበረው የዘረኝነት ቲዎሪ ለፋሺዝም መጠንሰስና በካፒታሊዝም ዕድገት ሂደት ውስጥ የዳበሩ የሚሊተሪና የጸጥታ ተቋማትን ለሱ በሚስማማ መንገድ ማዋቀርና በርዕዮተ–ዓለም ደረጃ ሊረጋገጥ የሚችልና፣ በተለይም በማህበራዊ ቀውስና በስራ-አጥነት የተደናገጠውን የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በመሳብ ተቀባይነት እንዲኖረውና እንደ ስርዓትም እንዲዋቀር ማድረግ ተችሏል። ጦርነትን በማካሄድና ሌሎች አገሮችን በሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ እንደተነሳው የጀርመኑ ናዚዎች አስተሳሰብ ባለፉት 70 ዓመታት በተለይም የአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም የዓለምን ማህበረሰብ ለመቆጣጠርና ዕድላቸውን ለመወሰን ሲል በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ለማሳመን በቅቷል። የጀርመን ናዚዎች ጀርመን በሁሉም አገር (Deutschland über alles= Germany all over the world) በሚለው አመለካከታቸው አገሮችን ለመውረርና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ምክንያት ለመሆን እንደበቁ ሁሉ፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተስፋፋው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች አምባገነናዊ ስርዓቶች እንዲዳብሩና ጭቆናም እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅቷል። በየአገሮች ውስጥ መንግስታት የሚጠቀሙባቸው የስለላና የመጨቆኛ መሳሪያዎች በሙሉ ከውጭ የመጡና ዋና ዓላማቸውም ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ ስርዓት እንዳይመሰረትና፣ የየግለሰቦችም ሆነ የጠቅላላው ህዝብ የማሰብና የመፍጠር ኃይል እንዳይዳብርና እንደሰው እንዳይኖር ማድረግ ነው። የመንግስትን መኪና የተቆጣጠሩትን መንፈሳቸውን በመሰለብና የሆነውን ያልሆነውን እንዲያደርጉ በማድረግ ወደ አውሬነት መለወጥ ነው። የመንግስትም መኪናዎች፣ ማለትም የሚሊተሪው፣ የስለላው፣ የፖሊሱና የሲቪል ቢሮክራሲው ስልጣኔን ሳይሆን፣ ድህነትን፣ ነፃነትንና ዲሞክራሲን የሚያስፈኑ ሳይሆኑ፣ ጭቆናን የሚያሰፍኑ ሆነው በመዘጋጀታቸው በቀላሉ በነጭ ኦሊጋርኪውና በኤክስፐርትነት ስም በሚመጡት በቀላሉ የሚታለሉና ኋላ-ቀርነትን የሚያጠናክሩ ሊሆኑ በቅተዋል። በዚህ መልክ የተዋቀሩት የአፍሪካ መንግስታት መኪናዎች ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በእነ ፕላቶን፣ እንዲሁም ደግሞ በታወቁት የሬናሳንስ ምሁራኖች፣ ከላይብኒዝ ጀምሮ ካንትና ሄገል ድረስ የተደረሰበትን መመሪያዎች፣ ማለትም ፍትሃዊነትንና ዲሞክራሲን ማስፈን፣ እንዲሁም አንድ ህዝብ በአገሩ ውስጥ እርግጠኝነት ተሰምቶት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ብለው ያስቀመጡትን መመሪያዎችና ቅድመ-ሁኔታዎች እንዲጥሱ ሆነው በመዘጋጀታቸው ይኸው እንደምናየው የብዙ አፍሪካ አገሮችና የአገራችም ዕጣ ድህነትና ጭቆና ሊሆኑ በቅተዋል።  ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማፍለቅና በማዳበር የሰለጠነ፣ በመተሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አገር መገንባት ሳይሆን፣ በመዋዕለ-ነዋይ ስም የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማስፋፋትና ጥሬ-ሀብትን በመቀራመት የአንድን አገር ህዝብ አቅመ-ቢስ ማድረግና አገርን ማዳከም ሊሆኑ በቅተዋል። ህዝብን ማሳቀቅና ክትትል ማድረግ፣ በሆነው ባልሆነው መወንጀል፣ በአምላክ ምስል የተፈጠረን የሰው ልጅ መንግስት የሚባለውን አካልና ተቆጣጣሪዎችን እንደ ልዩ ፍጡሮች አድርጎ እንዲመለከት በማድረግ ነፃነትን መግፈፍ የስትራቴጂው አንድ አካል ነው። ስለሆነም በዚህ ዐይነቱ በምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮችና በሶስተኛው ዓለም መንግስታት የተደረሰበትን ከሳይንስና ክፍልስፍና ጋር የማይጣጣም አገር አፍራሽና የሰውን ኃይል በታታኝ ፖሊሲና ግኑኝነት አሜን ብሎ መቀበል ነው። ይህንን ጥያቄ ውስጥ የሚያገባ የእግዚአብሄርን ቃል እንደመጣስ ይቆጠራል።  አክራሪም እየተባለ ይወነጀላል።

የሚነሳው ጥያቄ በተገለጸለትና አሳቢዎችና ገጣሚዎች፣ እንዲሁም ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች በፈለቁበት፣ ከዚህም በላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባደገበት እንደ ጀርመን በመሰለው አገር ለምን የናዚ ርዕዮተ-ዓለም ሊፈልቅ ቻለ? ለምንስ እንደ ፈረንሳይና እንግሊዝ በመሳሰሉት የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ብቅ ሊልና እንደ ስርዓት ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም? የሚለው ነው። አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች ለዚህ ዐይነቱ ጥያቄ የሚሰጡት መልስ፣ 1ኛ) የተገለጸለት የከበርቴው መደብ በሰፊው ለመዳበር አለመቻል ሲሆን፣ በ2ኛ) ደረጃ ደግሞ፣ በፕረሺያ ዘመን የተዋቀረው የበለጠ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ የነበረው የሚለተሪ አወቃቀር በቀላሉ እንደነ ሂትለር ለመሳሰሉት ተገዢና የእነሱን ርዕዮተ-ዓለም ተቀባይ እንዲሆን አድርጎታል የሚል ነው። በሚሊተሪው፣ በንዑስ-ከበርቴውና በአንዳንድ ምሁራኖች ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነትን ለማግኘት ይችል ዘንድ የጀርመን ዘር(Aryan Race) ከሁሉም የበለጠና እሱ ብቻ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለማፍለቅና ለማዳበር እንደሚችል፣ እንደጥቁር የመሳሰሉ ዘሮች ደግሞ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የተፈጠሩ አይደሉም ብሎ በመስበኩና ለማሳመን በመቻሉ ነው። ይህ አስተሳሰብ ዛሬም በአብዛኛው የነጩ ኤሊት የሚስተጋባና ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመጠቀምና ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ የነጭ ኦሊጋርኪውን የበላይነት ማረጋገጫ መሳሪያ ሊሆን በቅቷል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህ ዐይነቱ በጀርመን ፋሺሽቶች የዳበረው አስተሳሰብ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በአብዛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች በተለይም በሚሊታሪው፣ በስለላ መዋቅርና ኮንሰርቫቲብ ተብለው በሚጠሩት ፓርቲዎች ዘንድ ሲንፀባረቅ ይታያል። ሌሎች ፓርቲዎችም፣ እንደ አረንጓዴው የመሳሰሉትና የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች የዚህ አስተሳሰብ ሰለባ በመሆን በሊበራሊዝምና በነጻ ንግድ ስም አሳበው አብዛኛውን የሶስተኛውን ዓለም አገሮች፣ በተለይም የአፍሪካን ኤሊት ሲያሳስቱ ይታያሉ። 3ኛ) በሩሲያ ምድር በኋላ ደግሞ ሶቭየት ህብረት ተብሎ በሚጠራው አገር የመጀመሪያው በቦልሺቢኮች የሚመራው የሶሻሊስት አብዮት በመካሄዱና፣ ይህ ዐይነቱ አብዮት ይሁዲዎች ዓለምን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው የነደፉትና ተግባራዊ ያደረጉት አንደኛው ዕቅድ ሆኖ በመታየቱና፣ ከዚህም በተጨማሪ ይሁዲዎች በሁሉም ቦታ የነበራቸውን የላቀ ቦታ፣ በተለይም የንዑስ-ከበርቴውን መደብ ስላስፈራው በጊዜው የነበረውን ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ-አጥ ቁጥርና የመንግስትንና የአገዛዝን ቀውስ በመጠቀም ሊነሳ የቻለ ፋሺሽታዊ አገዛዝ ነው ብለው ይናገራሉ። አንዳንድ የተገለጸላቸውና ክሪቲካል አስተሳሰብ ያላቸው ይህንን ሀተታ በመቀበል፣ ይህን የመሰለው ፋሺሽታዊ ስርዓት ሊነሳና ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለውና የሚችለው በብዙ ቅራኔዎች ውስጥ በሚገኘውና ቀድመው የነበሩ ማህበራዊ ግኑኝነቶችን እየበጣጠሰ በመምጣትና ግለሰብአዊነትን ባዳበረ የካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ብቻ ነው ብለው ለማረጋገጥ ይሞክራሉ። በእርግጥም ፋሺዝም ቀደም ብለው በነበሩ እንደፊዩዳሉ በመሳሰሉ ስርዓቶች ውስጥ አልታየም። ስለሆነም ካፒታሊዝም የሰዎችን አስተሳሰብ በአንድ ዐይነት ርዕዮተ-ዓለምና የፍጆታ አጠቃቀም የመቅረጽና የሌሎችን አገሮች ባህልና ህብረተሰብአዊ ግኑኝነቶች እንዳለ የመደምሰስ ኃይል አለው። የሌሎችን አገሮች ታሪክ ሰሪነትና ለካፒታሊዝም ዕድገት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ በፍጹም አይቀበልም። ስለሆነም በዓለም ላይ ያለ ህዝብና መንግስታት በሙሉ ዓለም አቀፋዊ በሆነ መንግስትና ስርዓት መተዳደር አላቸው። እያንዳንዱ አገር የራሱን ኢኮኖሚና ባህል ለህዝቡ በሚስማማ መልክ ማደራጀትና ማዘጋጀት የለበትም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ እስካሁን የተደረሰበትን ስምምነትና የተፈጥሮ ህግ የሚጥስ ሰለሚሆን በአንዳች ዐይነት ነገር መወገድ አለበት። አልቀበልም ያሉና ታዛዥነትን የማያሳዩ መንግስታት የግዴታ በኃይል መወገድ አለባቸው። ይህ ዐይነቱ በግሎባል ካፒታሊዝም የተደነገገው አስተሳሰብ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚጥስ ነው። ተፈጥሮም ሆነ ማንኛውም ህብረተሰብ የልዩ ልዩ ነገሮች(Diversity) ጥምሮች ናቸው። ተፈጥሮም ሆነ ማንኛውም ህብረተሰብ ወደፊት ተከታታይነት ባለው መልክ ሊያድጉ የሚችሉት የተፈጥሮን ህግ መረዳት የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ዐይነት የአሰራር ኖርም፣ የአመጋጋብና የአኗኗር ባህል ማስፋፋት የግዴታ ባህላዊና ማህበራዊ፣ እንዲሁም ኢኮሎጂያዊ ቀውሶችን ያስከትላሉ። ለዓለም ሰላምና ለአገሮች ተከባብሮ መኖር አስጊ ሁኔታን ይፈጥራሉ። በሌላ ወገን ግን ካፒታሊዝም ውስጡ ባለው የስግብግብነትና የበላይነት ባህርይ የተነሳ የግዴታ የተፈጥሮንም ሆነ የህብረተሰብን ህግ የሚጥስ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ነው።

በመሆኑም ካፒታሊዝም የግዴታ ከአገሩ ውጭ የመስፋፋትና ሌሎችን አገሮች በቁጥጥሩ ስር የማድረግ ውስጣዊ ኃይል አለው። አይሎ ሊወጣ የቻለውም ከባሪያ ንግድና ከቅኝ ግዛት ጋር በመያያዙና በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የጥሬ-ሀብቶችን ለመቆጣጠር በመቻሉ ብቻ ነው። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት ሊስፋፋና ሊዳብር የቻለው የጥሬ-ሀብት አስፈላጊነት ግንዛቤው ውስጥ ከገባ በኋላ ነው። ምክንያቱም ካፒታሊዝም ሊያድግና ሊስፋፋ የሚችለው ለሀብት ክምችት(Capital accumulation)  መሰረት የሚሆኑ የጥሬ-ሀብቶችንና ርካሽ የሰው ጉልበት እንደልብ ሲገኙ ብቻ ነው።  ስለሆነም በተለይም ካፒታሊዝም ከፍተኛውን የዕድገት ደረጃ መያዝ ከጀመረበት ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ጀምሮ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ወደ ጥሬ-ሀብት አምራችነትና አቅራቢነት በመለወጥ ለብዙ መቶ ዓመታት የገነቧቸው ተቋማት፣ ባህላዊ መተሳሰሮችና ማህበራዊ ግኑኝነቱቶች እንዲበጣጠሱ በማድረግና አዲስ ዐይነት ለአውሮፓውያን የሚስማማ ብዝበዛንና ጭቆናን የሚያመቻች መንግስታዊ አወቃቀር በመመስረት በአውሮፓ ምድር ደግሞ ሀብት ሊዳብርና ቲክኖሎጂያዊ ምጥቀት ሊታይ ችሏል። ይህም ማለት፣ በአንድ በኩል በአፍሪካ ውስጥ ድህነትና ኋላ-ቀርነት መታየት፣ በሌላ ወገን ደግሞ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መታየት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ነው።

ካፒታሊዝም ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት አልፎ ወደ ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ሲሸጋገርና ከባንኮች ጋር እየተቆላለፈ በመምጣት የምርት ክንውን ከታች ወደ ላይና በአግድሞሽ (Vertical and horizontal forms of concentration of capitalist production and reproduction system) እየተደራጀ ሲመጣ ትናንሽ ኢንዱስትሪዎችን ማውደም ቻለ። የፋይናንስ ኢንዱስትሪና የትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መቆላለፍ ደግሞ የግዴታ በመንግስታትና በፓርቲዎች ላይ ጫና በማድረግ መንግስት ይበልጥ የትላልቅ ኢንዱስትሪዎችንና ባንኮችን ጥቅም የሚያስጠብቅና የሚያራምድ በመሆን ከአገር ውስጥ አልፎ በሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም እንደ አፍሪካ በመሳሰሉ በተፈጥሮ ሀብት በታደሉ አገሮች ላይ ጫና እንዲያደርግና በተለያዩ የኢኮኖሚ መሳሪዎች እንዲተበተቡ ለማድረግ በቃ። በተለይም በ1944 ዓ.ም ሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች፣ ማለትም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና (IMF) የዓለም ባንክ (WB) ከተቋቋሙ በኋላ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታትና ትላልቅ ኩባንያዎች እነዚህን ተቋማት ተገንና ሽፋን በማድረግ በላቲንና በማዕከለኛው፣ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ አገሮች ላይ ተፅዕኖ የማድረግና፣ ጥሬ-ሀብታቸውን ለመበዝበዝና ባሉበት ቀርተው እንዲቀሩ ለማድረግ ችለዋል። ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ለአፍሪካና ለተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው ለሚጠሩት አገሮች ረቅቀው የቀረቡትንና ተግባራዊ የሆኑቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና፣ በተለይም ደግሞ የመዋቅር ማስተካከያ (Structural Adjustment Program) በመባል የሚታወቀውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠጋ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ፣ ፖሊሲዎቹ በሙሉ በአንድ በኩል ሀብት በተለያየ መልክ ከአፍሪካና ከተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች የሚፈሱበትን መንገድ የሚያመቻቹ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ እነዚህ የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች በምንም መንገድ ወደ ውስጥ ያተኮረና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡና ራሳቸውን እንዳይችሉ የሚያደርግ ነው። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚሰጠውም ትምህርት፣ በተለይም የኢኮኖሚክስ ትምህርት የካፒታሊዝምን ዕድገት ሚስጥር ማንም ሰው እንዳያውቀው ሆኖ የቀረበና መማሪያ የተደረገ በመሆኑ ፖሊሲ አውጭዎች ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ይዘት የሌለውንና ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ያልረቀቀውን የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የባሰ ድህነትን የሚያስፋፉና ያለው ችግር እየተባባሰ እንዲመጣ የሚያደርጉ ሊሆኑ በቅተዋል።

ባጭሩ ግሎባል ካፒታሊዝም ልዩ ልዩ ተቋማትንና የጦርነት ድርጅቶችን በመመስረትና በማጠናከር ሌሎች ኃያል ከሚባሉ አገሮች ጋር ፉክክር በማድረግና ስማቸውን በማጉደፍ ከካፒታሊዝም በስተቀር ሌሎች አገሮች ለሰላምና ለዕድገት የቆሙና የሚቆሙ ኃይሎች አይደሉም በማለት በተወሳሰበ መልክ ማሰብ የማይችሉ መንግስታትንና አገዛዞችን በማሳሳት በየአገሮች ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ በቅቷል። ላይ ከተጠቀሱት ተቋማት በስተቀር፣ የስሜን አትላንቲክ የጦር ስምምነት፣ የዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት፣ የአውሮፓው አንድነትና በተባበሩት መንግስታት ስር የተደራጁትና በኢኮኖሚ ዕድገት ስም የተቋቋሙት ድርጅቶች በሙሉ ዋናው ተግባራቸው፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስክ አድገውና በልጽገው ለህዝቦቻቸው አለኝታ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው። በአጭሩ የእነዚህ ተቋማት ዋናው ዓላማ የነጭ ኦሊጋርኪውን የበላይነት መጠበቅና ለዝንተ-ዓለም ደግሞ የአፍሪካ አገሮችን ባርያ አድርጎ ማስቀረት ነው። በዚህም በዚያም ብሎ ማህበራዊ ውዝግብ መፍጠርና ስልጣን ላይ የተቀመጡት የባሰ አረመኔ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በአፍሪካ አገሮች ያሉ መንግስታትና የስለላ ድርጅቶችም ዋና ተግባር ከውስጥ ዲሞክራሲንና ነፃነትን በማፈን የብዝበዛውንና የድህነት ዘመኑ እንዲጠናከርና የሚጠናከርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።

ይህን ዐይነቱ የብዝበዛ ስርዓት የረቀቀ ከመሆኑ የተነሳ፣ በቀላሉ ማንኛውም ተራ ሰው ወይም በተራ አካዴሚክስ ዕውቀት የሰለጠነ ሊገባው በፍጹም አይችልም። ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሚል ስም የያዙ ድርጅቶች በሙሉ ተልዕኮአቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማስፋፋትና የህዝቦችን ኑሮ ማሻሻል ነው የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተቀባይነትን በማግኘቱ እነዚህ ተቁማት በረቀቀ መልክ በተለይም በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ድህነትን እንደሚያስፋፉና አምባገነናዊ አገዛዞች እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉ ለአብዛኛዎቻችን ግልጽ አይደለም። በመሆኑም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከስድሳዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ የፖለቲካ ነፃነት ተቀዳጁ ቢባልም በመሰረቱ ግን ከድሮው የብዝበዛ ስርዓት በፍጹም ሊላቀቁ አልቻሉም።  የየመንግስታቱ መኪናዎችና ገዢዎች ከቅኝ ግዛት አስተዳዳሪዎቻቸው ጋር በብዙ ሺህ ድሮች የተሳሰሩ በመሆናቸው ዋና ተግባራቸውም ምዝበራና ድህነት ስር እንዲሰዱ በማድረግ ህዝቦቻቸው በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ለማድረግ በቅተዋል። በየአገሩ ውስጥም ክሪትካል አመለካከት ያለው የዳበረና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በመደረጉና፣ አንዳንድ ምሁር ነን ባዮችም ከውጭ ዓለም ጋር በጥቅም የተሳሰሩ በመሆናቸው የውጭ ኃይሎች፣ መንግስታትንም ሆነ የገዢ መደቦችን በቀላሉ ሊያታልሉ ችለዋል። ምሁር ነኝ ባዩም ትችታዊ አስተሳሰብን (Critical Thinking) ለማዳበር ባለመቻሉ ለምንድነው አገራችን ለማደግ ያልቻለችው? የጥሬ-ሀብትና ለእርሻ መሬት የሚሆንና የተትረፈረፈ ሀብት እያለን ለምንድነው ወደ ኋላ የቀረነውና ለማኞችም እንድንሆነ የተደረግነው? ብሎ ስለማይጠይቅ ድህነቱና ኋላ ቀርነቱ ስር እየሰደዱ መምጣት ችለዋል ማለት ይቻላል። እንደዚህ ዐይነቱን ጥያቄ የሚያነሱና የካፒታሊስት አገሮችን ግፊትና ወደ ኋላ እንድንቀር የሚያደርጉትን የተወሳሰቡ መሳሪያዎች በግልጽ ለማሳየት የሚሞክሩትን ደግሞ በኮሙኒዝም ስም በመወንጀልና በማስፈራራት በአገራችን ምድር ዕውነተኛ የሆነ ምሁራዊ አስተሳሰብና ለተሟላ ዕድገት የሚያመች ዕውቀት እንዳይስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማድረግ ችለዋል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በተለይም በተማሪው እንቅስቃሴ ዘመን በኮሙኒዝም ስም ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ ሰዎች ዛሬ የቀኝ አቋም ወይም ፋሺስታዊ አዝማሚያ በመያዝ በአገራችን ምድር ቢያንስ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ አብዛኛውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል ሰፋ ያለ የገበያ ወይም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዳይገነባ አደገኛ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ነገሩን መቋጠሪያ ለማስያዝ፣ ዛሬ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ምድር የመንግስት መኪና ላይ የተቆናጠጡትና ምሁሮችም በራሳቸው ነፃ አስተሳሰብና ርዕይ የሚመሩ ሳይሆን የካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስት ታዛዦች ናቸው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ትችታዊ አመለካከት ያላቸው ምሁራን እነዚህን ኃይሎች ንቃተ-ህሊና የጎደላቸው የኢምፔሪያሊዝም መሳሪያዎች (The unconscious tools of imperialism) ብለው ይጠሯቸዋል። ወደ ምዕራብ አፍሪካ ስንመጣ ደግሞ 14 የሚጠጉ የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ነፃነትም ከተቀዳጁ በኋላ በፈረንሳይ ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። የፈረንሳይ በጀት ሙሉ በሙሉ በእነዚህ አገሮች የሚደጎም ነው። መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በየዓመቱ ወደ $ 600 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ፈረንሳይ አገር ይዘዋወራል፤ ወይም ደግሞ እነዚህ አስራ አራቱ የአፍሪካ አገሮች ከውጭ ንግድ የሚያገኙች የውጭ ምንዛሬ 60% የሚሆነው የፈረንሳይ ማዕከላዊ ባንክ ይገባል። እንደዚሁም ወርቃቸው እዚያው ነው የሚከማቸው። የእነዚህ አገሮች ገንዘብ ድሮ ከፍራንክ አሁን ደግሞ ከኦይሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በፊስካልና በሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ተዘግቷል። ይህን ዐይነቱን የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ተቃውመው የተነሱና የጥገና ለውጥ ለማድረግ የሞከሩ እንደ ሳንካራ የመሳሰሉ ወጣትና ካሪዝማ የነበራቸው መሪዎች በራሳቸው ጓደኞች እንዲገደሉ በማድረግ የብዝበዛውና የጭቆናው፣ እንዲያም ሲል ኋላ-ቀር የሆነው ስርዓት እንዲቀጥል ለማድረግ ተችሏል። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ደግሞ እንደቻይና ለመሳስሉት አዲስ ተስፋፊና ኃያል መንግስታት የጥሬ ሀብታቸውን ለመሽጥ የተገደዱ ወይም ቆፍረው እንዲያወጡ ስምምነት ያደረጉ እንደ ማሊ የመሳሰሉ አገሮች በእስልምና መስፋፋትና በአሸባሪነት ሽፋን ስም በአሜሪካን የሚመራው የምዕራቡ ዓለም አፍሪኮም የሚባል የጦር ኃይል በመገንባትና ዋናው ቢሮውን ሽቱትጋርት በሚባለው አንድ የጀርመን ከተማ ውስጥ በማድረግ ከዚያ ሆኖ ግልጽ ጦርነት እያደረገ ለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በዚህ ዐይነቱ የጦር አውታር ውስጥ ከአፍሪካ ውስጥ አንዳንድ መኮንኖች ተመልምለው በመግባት በራሳቸው በጥቁሩ ህዝባቸው ላይ ጦርነት እንደሚያካሂዱ የታወቀ ጉዳይ ነው። አንዳንድ የድሮው የኢትዮጵያ ወታደር አባልና ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸው ለዚሁ የአፍሪኮም የጦር ማዕከል እንደ አማካሪነትና መርሲነሪዎችን በመመልመል ኃላፊነት የጎደለው ስራ እንደሚሰሩ ግልጽ ነው። እነዚህ ኃይሎች እዚያው በዚያው ደግሞ ለአገራቸው ተቆርቋሪ በመምሰል ሲጽፉና ለየሚዲያኖች የቃለ-መጠይቅ መልስ ሲሰጡ ይደመጣሉ። እነዚህ መኮንኖች ከአሜሪካን ኢምፔያሊዝም ጋር የተቆላለፉ በመሆናቸው ከቻሉ እንደገና ስልጣን ላይ በመምጣት የጨለማውንና የጦርነቱን ዘመን ለማራዘም አጥብቀው እንደሚሰሩ የታወቀ ጉዳይ ነው።

ስለሆነም ከኮንጎ ዛየርና እስከማሊ ድረስ፣ እንዲሁም ደግሞ ሰሞኑን በሞዛቢክ በእስላም አሸባሪዎች ይካሄዳል የሚባለው ጦርነትና በመንግስታት መሀከል ያለው ግብግብ እነዚህ አሸባሪዎች ተቀማጭነታቸውን በምዕራቡ ዋና ከተማዎች ባደረጉ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች የሚደገፉና ጦርነቱም የውክልና ጦርነት ነው። ዋናው ዓላማውም የአፍሪካን ስትራቴጂክ የሆኑ ማዕድኖችን መቆጣጠር ሲሆን፣ ከረጅም ጊዜ አንፃር ደግሞ በምንም ዐይነት በእነዚህ አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሰፋ ያለና የሚባዛና የሚያድግ ኢኮኖሚ እንዳይመሰረቱ በሩን መዝጋት ነው። ከዚህም በላይ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችና እንደ ዓለም ባንክ የመሳሰሉት ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውን የኢኮኖሚ ፖሊስ ተግባራዊ እንዲሆን እያስገደዱ አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች እዚያው ቀጭጨው እንዲቀሩ ማድረግ ነው። አገሮችን በብድር መተብተብና የወለድ ወለድ ከፋይ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው ድህነትን መፈልፈያና የኋላ-ቀርነት ስትራቴጅ ነው። ከዚህ በመነሳት ነው በተለይም የአገራችንን በወያኔ የአገዛዝ ዘመን የሰፈነውን የምዝበራና ህዝብን የማድኸየት፣ እንዲሁም ደግሞ አገሪቱን በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል እርስ በርስ አለመተማመንና ዛሬ እንደምናየው ህዝባችን እንዲታረድ ለመደረግ የበቃውን ስርዓት መገንዘብ የሚቻለው። ስለዚህ የህውሃትን ወይም የወያኔን አገዛዝ ከምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም ወይም ከኢምፔሪያሊዝም ነጥሎ ማየት ትልቅ የታሪክ ወንጀል መፈጸም ብቻ ሳይሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገራችን ምድር ሰላም እንዳይሰፍንና ህዝባችን ነፃነቱን በመቀዳጀት በጋራ አገሩን እንዳይገነባ ትልቅ አሻጥር እንደመስራት የሚቆጠር ነው።

         

ህወሃት ፋሺሽታዊ ወይም የጁንታ አገዛዝ? ወያኔ የአሜሪካንና የእንግሊዞች ፕሮጀክት ወይስ የኢትዮጵያ መንግስት?

ህወሃት ወይንም ወያኔ በአሜሪካንና በእንግሊዝ ድጋፍ ስልጣን ላይ የወጣና የእነሱን አገርን የማፈራረስ ስራ የሚሰራው ነው ብሎ ኢትዮጵያኖችን ማሳመን በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደዚህ ብለው ሲነግሯቸው፣ እንዴት እንደዚህ ብለህ ደፍረህ ትናገራለህ፣ እነሱ እንደ ጌታችን እየሱስና ማርያም ወይም መልአከን መስለው የተፈጠሩ ስለሆኑ ተግባራቸው በሙሉ የሰውን ልጅ ከጥፋት ለማዳንና፣ በዚህች ዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን ሌት ተቀን ሳይታክቱ የሚሰሩ ናቸው ይሉናል። ታዲያ ይህ ከሆነ ለምንድነው የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በአውሮፓ ምድር ሊከሰቱና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መገደል ምክንያት ሊሆኑ የቻሉት? በምንስ ምክንያት ነው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ኮሙኒዝምን ለመዋጋት በሚል ሽፋን ከቬትናም ጀምሮ እስከአንጎላና ሞዛምቢክ ድረስ በሲአይኤና በሌሎች የስለላ ድርጅቶች የተደገፉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ሊካሄዱ የቻሉት? ብለው ሲጠይቋቸው፣ ይህ ሁሉ ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ የተካሄዱ ጦርነቶች ናቸው፤ እነሱን ካለአግባቡ መውንጀል ተገቢ አይደለም በማለት በዐይናቸን ያየነውንና የምናየውን፣ እንዲሁም ደግሞ በብዙ ኤክስፐርቶች የተረጋገጠውን አልቀበለም በማለት አጉል የኮሙኒስቶች ውንጀላና ስም ማጥፊያ ዘዴ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ።

እነዚህን የመሳሰሉ ምሁራን አመኑ አለመኑ፣ ተቀበሉ አልተቀበሉ ያለፈው ሰባ ዓመት የዓለም ፖለቲካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱትና የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አይደሉም። በሌሎች የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተነሱትንና የወደቁትን አገዛዞች፣ የመንግስት አወቃቀርና የጭቆናዎች ስር መስደድና ኋላ-ቀርነትና፣ በተለይም ደግሞ 27 ዓመታት ያህል ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ ፋሺስታዊ ድርጅት ወገኖቻችን ሲገድልና ሲያስር፣ እንዲሁም ሲያሰቃይ የከረመው ከኢምፔሪያሊዝም ጋር በጥብቅ በመተሳሰሩ የተነሳ ነው። የህዝባችንን ሞራል በማዳከምና አቅመ-ቢስ በማድረግ የለማኝነቱን ዘመን ለማራዘም ነው።

የህውሃት አነሳሰና ማደግ፣ እንዲሁም ስልጣን ላይ መውጣት ካለ እንግሊዞችና በኋላ ደግሞ ካለ አሜሪካኖች ድጋፍና የአስተሳሰብ ልገሳ ውጭ በፍጹም ሊታሰብ የሚችል ጉዳይ አልነበረም። ከዚህም በላይ አሜሪካኖች በኢትዮጵያ የስለላ መዋቅር ውስጥ ባይገቡና በወታደሩ መሀከል የነበረውን ግኑኝነት ለመበጣጠስ ባይችሉ ኖሮ ህወሃትም ሆነ ሻቢያ ድልን ሊቀዳጁና ስልጣን ላይ ሊወጡ ባልቻሉ ነበር።  ህወሃት ማርክሲስት ነኝ፣ የአልባኒያውን የሆጃን የሶሻሊስቱን መንገድ እከተላለሁ ብሎ የተነሳ ቢያስመስለውም፣ ከአንድ ጎሳ ብቻ መፍለቁና፣ በተለይም ደግሞ በጊዜው የነበረው አብዮታዊ ሂደት የግዴታ በእንግሊዞችና በአሜሪካኖች የስለላ ጉያ ስር እንዲወድቅና አስፈሪውን የጉግ ማንጉግ ስርዓት እንዲዋጋና ከእነሻቢያና ከሌሎች ፀረ-ህዝብና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በማበር ደርግን ጥሎ ስልጣን ላይ ለመውጣት ችሏል። በጊዜው በአንድ በኩል በወታደሩ አገዛዝ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በነፃ አውጭነት ስም በሚንቀሳቀሱት እንደ ህውሃት በመሳሰሉት መሀከል ይካሄድ የነበረው ጦርነት በመሰረቱ የውክልና ጦርነት ነበር ብሎ በእረግጠኝነት መናገር ይቻላል። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ እነ ህውሃትና ሻቢያ፣ ሌሎች በግራ ስም ይምሉና ይገዘቱ የነበሩት፣ እንዲሁም አንዳንዶች ካለ በቂ ጥናትና ምርምር በጭፍኑ ኮሙኒዝምን በመጥላት ከአሜሪካን ጋር በመሰለፍ ጦርነት ያካሄዱ የነበሩት ኃይሎች በሙሉ ዋና ዓላማቸው አዲስና የተሻለ፣ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ሳይሆን የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማሟላት ብቻ ነበር ጦርነት ውስጥ የገቡትና ለብዙ መቶ ሺህ ወታደሮችና ወጣቶች ዕልቂት ምክንያት ሊሆኑ የበቁት። የድንቁራናቸው ሰለባ የሆኑና የመጨረሻ መጨረሻም በአገራችን ውስጥ ምን ዐይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል? ብለው ለመጠየቅ ያልቻሉና፣ አገራችን ዛሬ እዚህ ዐይነቱ ምስቅልቅል ሁኔታ ላይ እንድትወድቅ ያደረጉ ናቸው። የለም ይህ የምትለው ሁሉ ትክክል አይደለም፤ የኛ ዋና ዓላማ ዲሞክራሲያዊትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ነበር ቢሉን፣ አንድን አገር ለመገንባት የግዴታ የእርስ በርስ ጦርነት ማካሄድ አያስፈልግም ነበር እንላቸዋለን። እህትንና ወንድምን እየገደሉና እያሳደዱ አገር መገንባት አይቻልምና እንላቸዋለን።

ለምን አሜሪካና እንግሊዝ፣ እንዲሁም ደግሞ የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች በኢትዮጵያችን ላይ ጦርነት ማወጅ ፈለጉ? ነገሩ ቀላል ነው። በጊዜው በሶሻሊስታዊ ስም የተካሄደው የጥገና ለውጥ በሙሉ በምንም መልኩ ከሶሻሊስት ጋር የሚያገናኘው ነገር አልነበረም። በጊዜውም የነበረው ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊናና በጣም ደካማ የሆነ የማቴሪያል ሁኔታ ለሶሻሊስት አብዮት አያመችም ነበር። በእነ ማርክስ ዕምነት የሶሻሊስት አብዮት ሊካሄድ የሚችለው በአንድ አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጹ የምርት ኃይሎች (productive forces) በከፍተኛ ደረጃ ከዳበሩና የሰውም የንቃተ-ህሊና በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከሆነ ብቻ ነው። ይሁንና ግን በማርክስ አስተሳሰብ ይህ ጉዳይ በተወሰኑ ወደ ኋላ በቀሩ፣ ይሁንና በህብረት ስራ በሚገለጹ (Communal relationship) አገሮች ውስጥ እንደየሁኔታው አብዮት ሊካሄድ ይችላል ይላሉ። ማርክስ እንደ ምሳሌም የሚጠቅሰው በጊዜው የነበረውን ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈውን በሩሲያ የሰፈነውን በማህበር ደረጃ በመደራጀት ይተገበር የነበረውን የእርሻ ምርት እንደምሳሌ በመውሰድ ነው። ይሁንና ራሺያም ሆነ እንደ ቻይና የመሳሰሉት ከካፒታሊስት አገሮች ጋር ሲነፃፀሩ ወደ ኋላ የቀሩ ስለነበሩ ከኋላ መያዝ የሚለውን ስትራቴጂ(Catching-up Strategy) በመከተልና አብዮት የሚለውን የርዕዮተ-ዓለም መመሪያ በማድረግና ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስና በማደራጀት አገራቸውን የመገንቢያ ስልት አድርገውታል ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ሰፊውን ህዝብ ማሰባሰብና ትላልቅ ፕሮጀክቶችን፣ የከተማና የካናል ሲይሰትም ግንባታዎች፣ እንዲሁም የቤተ-መንግስትና ትላልቅ ካቴድራል ስራዎችን ስንመረምር የካፒታሊስት አገሮች የኋላ ኋላ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ባለቤት በመሆን ወደ ካፒታሊዝም ማምራት የቻሉት በዚህ ዐይነቱ ሀብትንና የሰውን ጉልበት በማንቀሳቀስ ብቻ ነው። ካፒታሊዝም ወይም ደግሞ አዳም ስሚዝ የነፃ ገበያ ብሎ የሚጠራው ተግባራዊ ሊሆን የቻለው በረቀቀው እጅና (Invisible hand) በነፃ ገበያ አማካይነት አይደለም። የካፒታሊዝምም የተወሳሰበ ዕድገትና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ በእነ አዳም ስሚዝ ቲዎሪ ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም። ለካፒታሊዝም ስልተ-ምርት የሆኑ ቅድመ-ህኔታዎች በሙሉ ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን እስከ 18ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የፍጹም መንግስታት በሚባሉት ታውቆም ሆነ ሳይታወቅ የተዘጋጁና የኋላ ኋላ ለግለሰብ ፈጠራና ድርጊት ሁኔታዎችን ያመቻቹ ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር በአብዮት ስም የተካሄደው የጥገና ለውጥ በመሰረቱ ከኋላ-ቀርነት ለመላቀቅና አንድ የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሲባል ሰፊውን ህዝብ ከማንቀሳቀስና ከማደራጀት በስተቀር ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ነበር። ሰፋ ያለ ህብረተሰብአዊ (National Wealth) መፍጠር የሚቻለው በዚህ አማካይነት በሙከራና በልምድ በመሆኑ ብቻ ነበር። ይሁንና በቂ ግንዛቤ ያላገኘውና በምሁሩና በወታደሩ ዘንድ መብላላትንና ክርክርን ማግኘት ያልቻለው በአብዮት ስም የተካሄደው እንደ መሬት ላራሹ የመሳስሉት ለውጦችና ሰፊውን ህዝብ አደራጅቶ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ማንቀሳቀስ እንደ ትልቅ ወንጀል በመቆጠሩ ጦርነት ሊከፈትብን ችሏል። ከሌሎች አገሮች ልምድ እንደምናየውና፣ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ የሩሲያና የቻይና ልምድ እንደሚያረጋግጠው ይኸኛውን ከኋላ የመያዝ ስትራቴጂ የአገር ግንባታ መንገድ ባይከተሉ ኖሮ በፍጹም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ባልበቁ ነበር። ይሁንና በአንዳንዶች የሚነሳው ክስ ስታሊንና ማኦ ሴቱንግ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጨርሰዋል የሚል ነው። ይህ ትክክል ቢሆንምና በቀላሉ ሊገለጽ በማይችል የተወሰደ አላግባብ ድርጊት ቢሆንም የካፒታሊስቱ ዓለም ከዚህ ባላነሰ መልክ በአፍሪካና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ላይ ከፍተኛ ዕልቂት አድርሷል። በባሪያ ንግድ አማካይነት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተፈናቅሎ ፕላንቴሽን ስራ ላይ እንዲሰማራ ተደርጓል። በባርያ ንግድና በኋላ ደግሞ በቅኝ ግዛት አማካይነት አውሮፓ ከፍተኛ የሀብት ዘረፋ ለማድረግ ችሏል፤ በዚህም አማካይነት ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚያስፈልጉ የጥሬ ሀብቶች ከአፍሪካና ከተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች በግፍ ተግዘዋል። በዚህ አማካይነት ብቻ በአውሮፓ ምድር እያደገና እየተስፋፋ የመጣ የሀብት ክምችት ሊዳብር ችሏል። ከዚህም በላይ ከአውሮፓ ምድር በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ አውሮፓውያን ወደ አሜሪካ ሲሄዱና እዚያ መኖር ሲጀምሩ 17 ሚሊዮን የሚያህሉ እንዲያኖችን ጨርሰዋል። ከዚያ በኋላ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ጥቁር አፍሪካዊ ህይወቱን አጥቷል። በአገሩ ላይም በእኩል ደረጃ እንዳይታይ ሊደረግ በቅቷል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው ሰዎችን በማፈናቀል፣ ሀብታቸውን በመዝረፍ፣ በሌሎች አገሮች ውስጥ ደግሞ ጣልቃ በመግባትና ባነጠፈው የብዝበዛ መሳሪያ መሰረት ሀብት ከአፍሪካና ከተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ወደ አውሮፓና አሜሪካ በማስተላለፍ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በሶሻሊዝም ወይም በአምባገነንነት ስም የሚወነጀሉትን መንግስታትን በምንመለከት ጊዜ ለሀብት ክምችትና ለኢኮኖሚ ዕድገት ይሆናቸው ዘንድ አፍሪካንም ሆነ የተቀሩትን የሶስተኛው ዓለም አገሮች አልበዘበዙም። ባልተስተካከለ የንግድ ልውውጥና በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የእነዚህን አገሮች ኢኮኖሚዎችና ህብረተሰብአዊ አወቃቀሮች አላመሰቃቀሉም። በመንግስት ግልበጣም አልተሳተፉም። ይህ ጉዳይ በኢምፔሪካል ደረጃ የተረጋገጠና በህይወታችንም ዘመን ያየነው ሀቅ ነው። ከዚህ በመነሳት ነው በካፒታሊስት አገሮችና በሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ መሀከል ያለውን ግኑኝነት መመርመርና ፍርድ መስጠት የምንችለው።

ያም ሆነ ይህ በአገራችን ምድር ከሞላ ጎደል የጥገና ለውጥ የተካሄደ ቢሆንም ላለመሳካትና እንደዚያ ዐይነት የእርስ በርስ ጦርነት ሊከፈትብን የቻለው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም አጋጣሚ ሁኔታዎችን በማግኘቱና የአገራችንም ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። በተለይም የተለያዩ ድርጅቶችን መፈጠርና በነፃነት ስም መንቀሳቀሳቸው የመጨረሻ መጨረሻ የውጭ ኃይሎችን የጠቀመው። ስለሆነም እነዚህን የህዝብ ጠላቶች በመጠቀም ነው የህዝባችንን የማደግና የመሻሻል እንደዚሁም የነጻነት ፍላጎት የማፈን ዕድል ለማግኘት የቻለው።  ምክንያቱም ቀላል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከነቃና ከተደራጀ በዚህ አማካይነት ብቻ በራሱ ላይ መተማመን ይጀምራል፤ ቀስ በቀስም በኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ሊገነባ ይችላል። ስለሆነም ይህ ሂደት በአስቸኳይ መደናቀፍ አለበት የሚል ነበር የአሜሪካኖችም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ዓለም ስትራቴጂ።

ክዚህ ሀተታ ስንነሳ የህውሃት ስልጣን ላይ መውጣት ሎጂካዊ ነው። ይህን የመሰለው የህዝብና የአገር ጠላት ብቻ ነው የአሜሪካኖችንና የእንግሊዞችን አገርን የማፈራረስናና የህዝቡን ሞራል ማድቀቅ ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው። በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የጎሳ ፌዴራልዝም ዋናው ስትራቴጂ ነው። በዚህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው የዋር ሎርድ (War Lord) አስተሳሰብ በማዳበር አንዱን ጎሳ ከሌላው ጋር ማጋጨት የሚቻለው። ይህ ፖለቲካ በጣሊያን የወረራ ዘመን የተጠነሰሰ ቢሆንም ዕቅዱ እንግሊዞች እጅ የወደቀና የኋላ ኋላ ህውሃቶች እንዲጠቀሙበት የተደረገ ነው። ስለሆነም የፖሊሲው ተግባራዊነት ከአሜሪካኖችና ከእንግሊዞች ዕውቅና ውጭ ነበር ብሎ ማሰብ ከባድ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። በተለይም የኢትዮጵያ ሻለቃዎችና ዶክተሮች ይህንን ሀቅ በመካድና አዘናጊ አስተሳሰብ በማሰራጨት ነው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችንና እህቶቻችንን የሚያሳስቱት። ነገሩ ቀላል ነው። እነዚህ ኃይሎች በነጭ ጁንታ የአገዛዝ ሰንሰለትና መዋቅር ውስጥ የገቡና በአገራችን ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ፣ ይሁንና ደግሞ ሰፊውን ህዝብ የሚያስተሳስረውና ጥንካሬ የሚሰጠው አገር እንዳይገነባ በከፍተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ነው። እዚያው በዚያው ደግሞ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለትና ባንዲራ በማውለብለብ ብዙ ሰዎችን ያሳስታሉ፤ ተደማጭነትም አግኝተዋል።

አመንም አላመንም፣ ተቀበልንም አልተቀበልንም የተፈጠረው ሁኔታ ይህ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የሆነው ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የህወሃትንና የውጭ ኃይሎችን የምዝበራ ኃይል ያጠናከረና በዚያው መጠንም ህዝባችንን ያደኸየ ነው። በተግባርም የታየው ይህ ነው። እዚህና እዚያ ትላልቅ ፎቆችና ዘመናዊ የሚመስሉ፣ ግን ደግሞ የሰውን አስተሳሰብ የሚበታትኑ የገበያ አዳራሾች፣ በተለይም በአዲስ አበባ ምድር ቢገነቡም በምድር ላይ ያለው ሀቅ የሚያረጋግጠው 90% የሚጠጋው ህዝባችን በድብቅ ረሃብ እንደሚሰቃይ ነው። አብዛኛው ህዝብ ተከታታይ የሆነ ገቢ የሌለውና መጠነኛ ገቢ የሚያገኘው ደግሞ በሚያገኘው ወርሃዊ ገቢ የቤት ኪራይ ለመክፈልና ቤተሰቡን ለማስተዳደር የማይችልበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በየቦታው የተሰሩት አምስትና አራት ኮከብ ሆቴል ቤቶች ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ተመጣጥነው ያልተሰሩና፣ ቱሪስቶችን ለመሳብ ተብለው የተገነቡ በመሆናቸው ኃይልን፣ ውሃንና ሌሎች የምግብ ዐይነቶችን በከፍተኛ ደረጃ የሚጋሩ ናቸው። ስለሆነም በዚህና በፖሊሲው አማካይነት የተነሳ ከፈተኛ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር ተደርጓል። በአጭሩ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወያኔንና የካድሬዎችን ኃይል ያጠነከረ፣ በሀብት እንዲደልቡ በማድረግና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተሳሰር አገሪቱን እንዲመዘብሩ በማድረግ ፋሺስታዊ ስርዓት እንዲዘረጋ አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ነው። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ዋናው ዓላማ ይህ ነው። በነፃ ገበያና በሊበራላይዜሽን ስም አንድን አገር በዕዳ መተብተብና ባልተስተካከለ የንግድ ልውውጥ አማካይነት የንግድ ሚዛኑ እንዲዛባ በማድረግ ሀብት ከአንድ ደካማ አገር ወደ ካፒታሊስት አገሮች ማስተላለፍ ነው። ህወሃት 27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ሲገዛ የተከሰተው ሁኔታ ይህ ነው። የዕዳ መቆለል፣ የውጭ ንግድ ሚዛን መዛባትና የዋጋ ግሽበት መናር ከሰማይ ዱብ ያሉ ነገሮች ሳይሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ውጤቶች ናቸው።

ወደ መንግስት መኪናም ስንመጣ በተለይም የወታደሩና የስለላ ድርጅቱ ከፍተኛ ሹማምንቶች በሙሉ ከአንድ ጎሳ የተውጣጡና፣ በዚህ አማካይነት በአንድ በኩል ጭቆናንና ግድያን ሲያስፋፉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በምዝበራ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ የናጠጡ ናቸው። ተበድለን ነበር፤ ተጨቁነን ነበር፤ እስካሁን ድረስ ሲገዛን የነበረው ከአማራው የተውጣጣና የአማራን ብሄረሰብ ጥቅም የሚያስጠብቅ የገዢ መደብ በመሆኑ አሁን ደግሞ ጊዜው የእኛ ነበር በማለትና የተሳሳተ ትረካ በማውራትና የትግሬን ብሄረሰብ በማሳሳት፣ በጠቅላላው በአገሪቱ ምድር ላይ የምዝበራንና የጭቆናን ስርዓት አስፈነው ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህም በላይ የትግሬ ብሄረሰብ ከሁሉም ብሄረሰብ የበለጠና በወርቅ የተፈተነ ነው በሚል ከናዚ ርዕዮተ-ዓለም የማይተናነስና የጌስታፖ አስተሳሰብን በማዳበር ከናዚዎች ያላነሰ ወንጀል ፈጽመዋል ማለት ይቻላል። በተለይም በወልቃይትና በጸገዴ ህዝብ ላይ የደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀልና፣ ስልጣን ከያዙበት ቀን ጀምረው የሚጠራጠሩትንና እንቅፋት ይሆነናል ብለው ያሰቡትን ሁሉ አሰቃቂ  በሆነ መልክ ይገድሉ የነበረው ከዚህ ዐይነቱ ፋሺስታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው።  በዚህ ዐይነቱ ምዝበራና ፋሺሽታዊ ድርጊት አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ተባብረዋል። ለወያኔ አስፈላጊውን ህዝብን ማሰቃያና መሰለያ መሳሪያ ሰጥተውታል፤ ካድሬዎቹንም አሰልጥነውታል። በአጭሩ ሰለጠንኩኝ የሚለው የነጩ ኦሊጋርኪ መደብ እንደዚህ ዐይነቱን መንፈሰ-አልባ አገዛዝና ብሄራዊና ሰብአዊ ስሜት የሌለውን ዘራፊ አገዛዝ በመጠቀም አንድ ጓደኛዬ እንዳለው „አገራችንን ወደ ሽንትቤትነት ለመለወጥ የቻሉት። ይህ ነው ከሬናንሳ ጀምሮ እስከሬፎርሜሽንና እስከ ኢንላይተንሜንት የተካሄደበት አውሮፓ የመጨረሻ መጨረሻ ውጤቱ። የመሸውና ልዩ ዐይነት የክርስትና ቫልዩ አለው የሚባለው አሜሪካና ግብረአበሮች በዚህ ዐይነቱ ፖለቲካቸው ያረጋገጡት ኢሞራላዊ እንደሆኑ ነው። በስግብግብነትና በበላይነት መንፈስ የሚመሩና በዓለም አቀፍ ደረጃም ይህንን የመሰለውን የተበላሸ ኢ-ሰባዊና ኢ-ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ነው በአገራችን ምድር እንዲስፋፋ ያደረጉትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማባላግ አገሪቱ እንድትበወዝ ለማድረግ የበቁት።

ከላይ በሰፊው ከተዘረዘረው ትንተና ስንነሳ ወያኔን ጥቁር ጁንታ እያሉ መጥራቱ ጠቅላላውን ድርጊቱን አሳንሶ እንደማየት ነው የሚቆጠረው። በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ጁንታዎች ታይተዋል። እነዚህ ሁሉ እርቀው በመሄድ እንደ ወያኔ የተወሳሰበ ሂትለራዊ ዐይነት የጭቆና ስርዓትና ጭፍጨፋ አልገነቡም። አገራቸውንም እንደዚህ አላስናቁም። ስለሆነም ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ምድር በውጭ ኃይሎች የተደገፈና ይረዳ የነበረ ፋሺስታዊ አገዛዝ ሰፍኖ ነበር ብሎ መቀበል ያስፈልጋል። በዚህ ስንስማማ ብቻ ነው ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለተስተካከለ ዕድገት መታገል የሚቻለው።

                     ከወያኔ መወገድ በኋላ የተፈጠረው ሁኔታና የነጩ ጁንታ መወራጨት!

በሁላችንም ዘንድ የወያኔ አገዛዝ መወገድ ተቀባይነትን ያገኘ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ደግሞ የለውጥ ኃይሎች የሚባለውና በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ ምን ዐይነት ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይከተል ይሆን ብለን በጥርጣሬ ዐይን እንመለከት የነበርን ጥቂቶች አይደለንም። በአንዳንዶችንም ዘንድ በመጀመሪያው ወቅት ተቀባይነትን ያገኘው „የለውጥ ኃይል“ የሚባለው ቀስ በቀስ በተግባር ያረጋገጠው ሆን ተብሎ ይሁን አይሁን ተበድዬና ተዋርጄ ነበርኩ፣ አሁን ደግሞ ተራው የኔ ነው በማለት የውሸት ትረካ የሚያወራው ኃይል የበላይነትን ያረጋገጠበት ሁኔታ ነው። በተለይም ለኦነጎችና በሳውዲ አረቢያና ግብጽ እንዲሁም በሲአይኤ የሚደደገፈው እንደጀዋር የመሳሰሉት ኃይሎች የፖለቲካውን ሜዳ በመቆጣጠርና ደረታቸውን ነፍተው እዚህና እዚያ በሚራውጡበት ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳለ ተስፋውን ቆርጦ ነበር ማለት ይቻላል። የፖለቲካውን ሜዳ ሆን ተብሎ ለእነዚህ ኃይሎች ይለቀቅ አይለቀቅ ማረጋገጥ ባይቻልም፣ የፖለቲካውን ሂደት ለተከታተለ የአንድነት አመለካከት ያላቸውን ኃይሎች፣ በጎጠኝነት አስተሳሰብ ወይም ደግሞ በአህዳውያን ስም በመወንጅልና ኃይላቸውን በመበታተን በለውጥ ሽፋን ስም ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ልክ ህወሃት ያካሄድ የነበረውን የምዝበራና የጭቆና ስርዓት በማስፈን በተለይም የኦሮሞን የበላይነት ለማረጋገጥ ነው። ይህንን ግልጽነት የጎደለውንና በተለይም ደግሞ አማራውን ለማዳከም ተብሎ የተካሄደው ፖለቲካና አማራውን እንደ ዋና ጠላት አድርጎ ያነጣጠረው ሂደት ለወያኔዎች መንሰራራትና ሲይሰተማቲክ ጭፍጨፋና የአገር ውድመት አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣  አገር ሲያተራምስ፣ ሲበዘብዝና ብዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን ሲገደል በነበረው የህውሃት ኃይል ላይ ጠቅላላውን ህዝብ አስተባብሮ በአንድነት በመነሳትና ሰላምን የሚያስፍና ህዝባችን እርግጠኝነት እንዲሰማው ስትራቴጂካዊ የሆነ ፖለቲካ ከመከተል ይልቅ የለውጥ ኃይሎችና ጽንፈኞች አሁንም ሆን ብለው የያዙት ስራ አርባ ዓመት ያህል ሲገደል፣ ሲገረፍ፣ እስር ቤት ሲወረወርና ከመሬቱ ሲፈናቀል በነበረው የአማራው ብሄረሰብ ላይ ነው ኃይላቸውን አስተባብረው የተነሱት። አሁንም በሌላ አነጋገር፣ ለኦሮሞ ጽንፈኞችም ሆነ ለኦዴፖ ዋናው ስትራቴጂክ ጠላት ሲገድላቸውና ከመሬታቸው ሲያፈናቅላቸው የነበረው ወያኔ ሳይሆን አማራው ነው። ግራ የሚያጋባና ሁኔታዎችን ለማገናዘብ የማይችል ጭንቅላት እንዳላቸው ኦዴፓና ተከታዮቹ አረጋግጠዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ኦዴፓዎች ክልላቸውን ያስተዳድሩ በነበረበት 27 ዓመት የኦሮሞን ልጅአገረዶችና ወጣቶችን ለፈረንጆች በባርነት ደሞዝ ተቀጥረው አበባ እንዲተክሉ፣ እንዲኮተኩቱና በኋላ እየቆረጡ አስተካክለው ለፈረንጁ ዘራፊ ኃይል እንዲሰሩ ያደርጉ የነበሩት አማራዎች ሳይሆኑ ራሳቸው የኦሮሞ የገዢ መደቦች ነበሩ። ሀቁ ይህ ከሆነና ቢያንስ 27 ዓመት ያህል የህውሃት አጋር በመሆን ራሳቸው ኦሮሞዎችን ከመሬታቸው ያፈናቀሉና የባርነት ስራ እንዲሰሩ ያደረጉ መሆናቸው እየተዋቀ ወያኔን ሳይሆን ለምን አማራውን እንደ ዋና ጠላት ለማየት እንደቻሉ ግራ የሚያጋባ ቢመስልም፣ እነዚህ ሰዎች ተጨባጭ ሁኔታዎችንና ለማንበብና የፖለቲካ አወቃቀርን በደንብ ለመተንተን እንደማይችሉ ነው ያረጋገጡት። ስለሆነም ተደረገ የተባለውን ለውጥ ለራሳቸው መጠቀሚያ በማድረግና፣ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የበላይነትን ቦታ በመያዝና መሬትን በመቀራመትና ሌሎች ሀብቶችን በመቆጣጠር የህውሃትን ወይም የጥቁር ጁንታውን ቦታ እየያዙ ሊመጡና ህብረተስቡን ሊያተራምሱ ችለዋል። እነዚህ አዲሶቹ ጁንታዎች የግሎባል ካፒታሊዝምና የነጭ ኦሊጋርኪው አሸከር በመሆን በተለይም በአማራውና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ በመነሳት የዘር ማጥፋት ስራ እያከናወኑ ለመሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ አደገኛ ተግባራቸው የአረጋገጡት በአማራውና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በጥቁር ህዝብ ላይ የተነሱ በዝቅተኛ ስሜት የተካኑና ምንም ዐይነት ምሁራዊ መሰረትና የሞራል ብቃት እንደሌላቸው ነው። አንዳንዶች ፍልስፍናና ሶሶዮሎጂ የተማሩ ቢሆኑም በተግባር የሚያሳዩት ግን ፊደል ያልቆጠረ ሰው እንኳ ሊያደርግ የማይችለውን ነው።

ይሁንና ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና አትኩሮ ከሃጫሉ መገደል በኋላ የፖለቲካውን ሜዳ በአዲስ መልክ እንዲበወዝ ለማድረግ ቢችልም ፖለቲካዊ ውዥንብርነትና የበላይነትን ለመያዝ መሯሯጥ አሁንም ድረስ ጋብ ያለ አይደለም። በእነጃዋር መታሰር የፖለቲካው መድረክ ለተወሰነ ጊዜ ጸጥታ ያገኘ ቢመስልም፣ አሁን ደግሞ አገርሽቶበት ልዩ ዐይነት መልክ እየያዘ በመምጣት ላይ ይገኛል። በተለይም ወያኔ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረገው አሳዝኝ ድርጊት በኢትዮጵያው ወታደራዊ ኃይል፣ በአማራው ክልላዊ ኃይልና ፋኖዎች ትብብር ከከሸፈና የወያኔም የክልሉ ልዩ ኃይል በማያዳግም መልክ ከተደመሰሰ በኋላ እነታዬ ደንደአ፣ ሺመልስ አብዲሳና ሌሎች የኦርሞ ጽንፈኞችና በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የተሰገሰጉ አደገኛ ኃይሎች በወታደሩ ላይ የደረሰውን ዕልቂትና የትግራይን ክልል ከፋሺስቱ የወያኔ ኃይል ነፃ ለማውጣት የተከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት በመዘንጋት የወልቃይትና ጸገዴ ነገር በእኛ ነው ሊወሰን የሚችለው በማለት የማያገባቸውን አደገኛ የፖለቲካ ቁማር መጫወት ጀምረዋል። አርባ ዓመት ያህል፣ በተለይም ደግሞ በ27 ዓመት በፋሺስቱ የወያኔ አገዛዝ ዘመን የራያና የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ተሰቃይቷል፤ እንደልቡ የአማርኛን ቁንቋ እንዳይናገርና በአማርኛም እንዳይዘፍን ክትትል ይደረግበት ነበር። ቁጥሩ የማይታወቅ ኃይል እየታፈነ በመወሰድ የት እንደተሰወረ አይታወቅም። አብዛኛው እንደተገደለ ይነገራል። ይህ ሁሉ ግፍና ስቃይ ከደረሰና ብዙ ወጣትም ህይወቱን ከሰዋ በኋላ የተቀረው ህዝብ አሁን እፎይ ማለት ሲጀምር የወልቃይትን ጉዳይ የወልቃይት ህዝብ አያገባውም ብሎ መናገርና ቅስቀሳ ማድረግ አጉል ጥጋብና ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመገንዘብ አለመቻል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን ደግሞ ሱዳን በግብጽና በሌሎች መንግስታት ድጋፍና ግፊት የአገራችን መሬት ውስጥ ሰተት ብላ ከገባችና የተወሰነ መሬት በቁጥጥሯ ስር ባዋለችበት ጊዜ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለማሰራት በሚል ሽፋን ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውን የታሪክ ቅርጽ የሆነ ህንጻ በማፍረስ እነ አቶ ሺመልስ አብዲሳና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑት በእብሪት የኢትዮጵያን ታሪክ በማፈራረስ ላይ ይገኛሉ። የራሳችውን ታሪክ መስራት ይፈልጋሉ። በሌላ ወገን ግን ሌላውን ህዝብ የሚያገልና ባይተዋር የሚያደርግ ፖለቲካ በመሰረቱ ፖለቲካ ሳይሆን የሽፍጠኝነት ስራ ነው። በመሰረቱ ፖለቲካ ሲባል በአንድ አካባቢ የሚኖርን ህዝብ ከፈለገው ብሄረሰብ ይምጣ ወይም ይወለድ ለአንደኛው ወገን ሳያደሉ ፍትሃዊነት የተሞላበት ስራ መስራት ነው። ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወለዱና  በአንድ ከተማም ሆነ መንደድር በሚኖሩት መሀከል መግባባት እንዲፈጠር ሁሉም በየሙያውና በፈለገው መስክ ሊሰማራበት የሚችልበትን ፕሮጀክት በመንደፍ ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ስራ መስራት ነው። ፖለቲካ ሲባል በአንድ አካባቢ የፈጠራ ስራ እንዲዳብር በልዩ ተቋማት የሚደገፍ የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። ከዚህም በላይ ለወጣቱ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መክፈትና ከጨረሰም በኋላ ስራ ሊያገኝ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ማለት  ነው። ባጭሩ ፖለቲካ ሲባል የሰለጠነና ተከታታይነት የሚኖረው ስራ መስራት ማለት ነው። ሰላምንና ዲሞክራሲን የሚያሰፍንና እያንዳንዱ ዜጋ በእርግጠኝነት የሚኖርበትን ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው። ባጭሩ የአንድ መንግስትም ሆነ የክልል አስተዳደር ኃላፊነትና ግዴታ ይህ መሆን አለበት። እነ ሺመልስ አብዲሳና የቤኔሻጉል አስተዳዳሪዎች ነን የሚሉት የተቃራኒውን ነው የሚሰሩት። ፖለቲካ ሲባል ደረት መንፋትና ዘር ተኮር ፖለቲካ ማካሄድ አይደለም። ይህንን ዐይነቱን እብሪት የተሞላበት ፖለቲካ ስንመለከት ለመሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብና ታሪኩን የሚወክልና የሚከላከል መንግስት አለ ወይ? ብለን መጠየቃችን አልቀረም።

በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችን ምድር ዕውነተኛና ተከታታይነት ያለው ፖለቲካ ሲካሄድ አይታይም። አገራችንና ህዝባችን የታሪክን ምንነት በተገነዘቡና አርቀው በሚያስቡ ሰዎች የምትተዳደር አይደለችም። ከሩቅ ሆነን  ከዚህም የባሰ  የሚያስፈራ ፖለቲካ እንደሚሰራ እየተመለከትን ነው። እናቶቻችንና አባቶቻችን የተዋደቁላትን አገር በመዋዕለ-ነዋይ ስም መሬትንና ፓርኮችን ለአንዳንድ አረብ አገሮች ለመሸጥ ሽር ጉድ ሲባል እንሰማለን። የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ህገ-መንግስቱን በመጣስና የህዝብ ተወካዮችን ሳያማክርና ክርክር ሳይደረግበት የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነት የሚያስገፍፍና ነፃነታችንን የሚያሳጣ አደገኛ ፖለቲካ በማካሄድ ላይ ነው። ዶ/ር አብይ ህገ-መንግስቱን በደንብ አንብበውት ከሆነ ህገ-መንግስቱ አንድ ሰው ብቻ መንግስት ነው አይልም። እንደ አገዛዝ የሚጠቃለሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩና የካቢኔት ሚኒስተሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ወይም ፓርሊያሜንትና ህግን አስፈጻሚው አካል ናቸው። እነዚህ ሶስት አካሎች(Organs) እንደ አገዛዝ የሚታዩና ተጠያቂነታቸውም ለጠቅላላው ህዝብ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆነ የተቀሩት የካቢኔት ሚኒስተሮች እንደ አስፈላጊነቱ ያከናወኑትን ስራና ለማከናወን ያልቻሉትን ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በየጊዜው ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስተሩም በፓርላሜንቱ ፊት የመጠየቅ ግዴታ አለባቻው። ጠቅላይ ሚኒስተር ስለሆንኩ ልትጠይቁኝ አትችሉም ሊሉ አይችሉም። ማንኛውም ከሌሎች አገሮች ጋር የሚካሄድ የፖለቲካ፣ የንግድና የመዋዕለ-ነዋይ ስምምነት ፓርላሜንቱ ሳይወያይበት ወደ ስምምነት መደረስ የለበትም። ጥቅሙና ጉዳቱ በፓርላሜንቱ ብቻ የሚመረመር ወይም የሚጠና ሳይሆን በእያንዳንዱ ነገር ላይ በቂ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች በመመደብ ማጥናትና የመጨረሻ መጨረሻ ጥቅሙንና ጉዳቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቅረብ አለበት። ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል፣ ጥቅሙ ይበልጣል ብሎ ፓርሊያሜንቱ ከአፀደቀ ብቻ ነው ጠቅላይ ሚኒስተሩ በስምምነቱ መሰረት ፊርማ ሊፈርም የሚችለው።  ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆነ የካቢኔት ሚኒስተሮች ህገ-መንግስቱን የሚፃረር፣ የአገርን ብሄራዊ ነፃነት የሚጎዳ ስራ የሚሰሩ ከሆነ በፓርሊያሜንት አጣሪ ኮሚቴ የመጠየቅ ግዴታ አለባቸው፤ ማብራሪያም መስጠት አለባቸው። አጣሪ ኮሚቴዎች ግድፍት የሚያገኙ ከሆነና በአገር ላይ አደጋ ይደርሳል ብለው ካመኑ ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆነ ሌሎች የካቢኔት ሚኒስተሮች ከስልጣናቸው መነሳት አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆነ ሌሎች የካቢኔት ሚኒስተሮች ስልጣን ሲሰጣቸው በፓርላያሜንቱ ፕሬዚደንት ፊት ቆመው ህገ-መንግስቱን በመያዝ የማሉትና የተገዘቱት ነገር አለ። ይኸውም ካለምንም አድልዎ የኢትዮጵያን ህዝብ አገለግላለሁ፤ በአገራችንና በህዝባችንም ላይ ማንኛውም ዐይነት አደጋ እንዳይደርስ አደርጋለሁ፤ ወይም አደጋው በጣም ትንሽ እንዲሆን አደርጋለሁ የሚል ነው። እንደምመለከተው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስተሩና የካቢኔት ሚኒስተሮች፣ እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች የሚባሉት መብታቸውንና ግዴታቸውን በደንብ የተረዱት አይመስልም። የአብዛኛዎች አፍሪካ አገሮች አገዛዞች ችግር እዚህ ላይ ነው። ስራቸው ምን እንደሆነ አለማወቅ፤ መብታቸውንና ግዴታቸውን አለመረዳት።፡

ያም ሆነ ይህ አንድ አገርና ህዝብ የቁማር ፖለቲካ የሚካሄዳበቸው አይደሉም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሰለችና የጥንት ታሪክ ያላት አገር ወዳድና ባህሏን የሚያስጠብቅላት አመራር ያስፈልጋታል። አገራችን ታሪክ በሌላቸውና የሰውን አገር ታሪክ በሚያበላሹ የውጭ ኃይሎች ማንነቷ እንዲጠፋ መሆን የለበትም። ይህ ዐይነቱ የቁማር ፖለቲካ በዚህ መልክ የሚቀጥል ከሆነ አገራችን በቀላሉ ልትወረር ትችላለች። አንድ አገር ውስጣዊ ጥንካሬ ማግኘት የምትችለው በህዝቡ መሀከል መተማመንና መተሳሰብ ሲኖር ብቻ ነው። የህዝቡን መንፈስ ሊያጠንክር የሚችል የአገር ግንባታ ሲካሄድ የዚያን ጊዜ ጠቅላላው ህዝብ በራሱ ላይ ይተማመናል። ከተማዎችና መንደሮች በስነስርዓት ሲገነቡ፣ በየቦታው እንደምጣኔ ሀብት ሁኔታ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የንግድ ልውውጥ ሲካሄድ ህዝቡም አገሩን ይበልጥ ይወዳል። እንደዚህ ዐይነት ህዝብም በውጭ ኃይሎች ይከበራል፤ ይፈራልም። ይሁንና እስካሁን ድረስ የሚካሄደው ፖለቲካ ህዝቡ አገሩን እንዲጠላ የሚያደርገው ነው፤ የሚያስንቀውና እንዲስደድ የሚያደረገው ነው። አንድ ህዝብ እየታረደና ከአካባቢው እየተፈናቀለ ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ „ህዝባችን ከተጠናከረ ማንኛውንም ከውጭ የሚመጣብንን ጠላት መክቶ መመለስ ይቻላል“ የሚለው የጠቅላይ ሚኒስተራችን አነጋገር ሎጂክን የተከተለ አይደለም፤ በዕውነተኛ የፖለቲካ ሳይንስ መነጽርም ሲመረመር ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ያልቻለ አባባል ነው። ለአንድ ህዝብ መጠናከር የግዴታ መንግስት ራሱ የጠቅላላው ህዝብ አለኝታ ሲሆንና፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትም የሚፈለግባቸውን ግዴታ ከተወጡ የግዴታ ህዝባዊ መተሳሰርና መጠናከር ይኖራል። ህዝባችንና አገራችንም በቀላሉ በማንም የውጭ ኃይል አይደፈሩም። ይሁንና ግን መንግስትም ሆነ የየክልሉ አስተዳዳሪዎች የሚሰሩት ስራ ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው። ፖለቲካቸው „የውጭ ኃይሎች ሆይ ኑና ውረሩን“ የሚል የጥሪ ግብዣ ነው የሚመስለው።

ያም ሆነ ይህ ወያኔ በማያዳግም ሁኔታ ከተመታ በኋላ እንደነታዬ ደንደአና ሺመልስ አብዲሳ የመሳሰሉት ፋሺሽታዊ ኃይሎች አደገኛ ሁኔታን እየፈጠሩ ነው። በዚህ ዐይነቱ አደገኛ አካሄዳቸው የማዕከላዊ መንግስት እጁ ይኑርበት አይኑርበት ማረጋገጥ ባይቻልም ዝም ብሎ ማለፉና አንድ ዐይነት የፖለቲካ አቅጣጫ ለመስጠት ፍላጎት አለማሳየቱ የሚያስጠረጥረው ነው። ጠቅላላውን ፖለቲካ አስመልክቶ በቀጥታ በጦር ሜዳ ላይ ከተሰለፉትና አመራር ከሰጡት ጄኔራሎች የተሰጠው ብልህ የሆነ ማስጠንቀቂያና ማሳሳቢያ የኢትዮጵያ ፖለቲካና መንግስት የፓርቲዎች መጫወቻ ሀብት ሳይሆን ሚዛናዊነትና ጥበብ የተሞላበት ስራ የሚሰራባቸው መሆን አለባቸው የሚል ነው። የፖለቲካ ሽኩቻና የስግብግቦሽ ፖለቲካው አቁሞ የግዴታ ወደ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለ-ገብ ዕድገት ዐይናችንና አዕምሮአችንን እናዙር የሚል ጥሪ ነው። ይሁንና ብልህ የተሞላበትን ጥሪ ለመገንዘብ ያልቻሉት የብልጽግናን ፓርቲ ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችና የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪዎችና አፈ-ቀላጤዎች ከቤኔሻጉል ክልል „አስተዳዳሪዎች“ ጋር በማበር በአማራውና በተቀረው የዋህ በሆነው ኗሪ ህዝብ ላይ በመነሳት ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በተለይም በመተክል በየቀኑ ብዙ ህዝብ እየተፈናቀለና እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልክ እየተገደለና ድረሱልኝ እያለ ጩኸት ቢያሰማም በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ ይህንን ድርጊት በሚያስተባብሩትና ንፁህ ዜጋን በአሰቃቂ ሁኔታ በሚገድሉት በአንዳንድ የኦሮሞ ክልልና የቤኔሻጉሎ አስተዳዳሪዎች ላይ ምንም ዐይነት እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት አላሳየም። ይህ ዐይነቱ ለማንም የማይጠቅም ጨዋታ እስከመቼ ነው መቀጠል ያለበት? ምን ያህልስ ሰው መገደል አለበት? ምስኪኑን ህዝብስ በመግደል የሚገኝ ደስታና ሀብትስ የቱን ያህል ሊያዝናና ይችላል?  የዛሬዎቹ አባወራዎች ለምን ከህውሃቶች ፋሺስቶች አይማሩም? በዚህ ድርጊታቸው ለዝንተ-ዓለም ተዝናንተው መኖር ይችላሉ ወይ?

በዚህ ዐይነቱ ዘር ተኮር ፖለቲካችሁ የመጨረሻ መጨረሻ የውጭ ኃይሎችን ነው የምትጠቅሙት። በተጨባጭ የምትሰሩትም ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎችና ለአረቦች ነው። አብዛኛዎቻችሁ ከውጭ ኃይሎች ጋር ግኑኝነት ያላችሁና ያለንን የጥሬ ሀብት መጥተው እንዲቀራመቱና ህዝባችንን ባሪያ እንዲያደርጉ ሌት ተቀን እየሰራችሁ ለመሆኑ የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ወያኔ 27 ዓመት እጅና ጓንቲ ሆኖ ሲሰራ የነበረው ከአሜሪካንና ከእንግሊዝ እምፔሪያሊስት ኃይሎች ትዕዛዝ በመቀበል ነበር። የሌሎችም የዓለም አቀፍን ስም የተከናናቡ ሎሌ በመሆን አገራችንን አስመዝብሯል፤ ህዝባችንንም አስንቋል። ራሳችውም ፈረንጆች ብዙ ዐመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩና ጥሩታ ከወጡ በኋላ አገራቸው ሲመለሱ ይህንን ነው የሚነግሩን። ለመሆኑ እናንተ ኢትዮጵያኖች ምን ነካችሁ? ታሪክስ አልነበራችሁም ወይ? እያሉን ነው የእንቅጩን የሚነግሩን። ያም ሆነ ይህ በብዙ ሺህ ሰዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሲሰቃዩና ሲገድሉ ሰለጠንኩ የሚለውና ሞራል የሌለው የኢምፔሪያሊስት ኃይል ድምጹን ያላሰማውና የማያሰማው አገራችንን እንደፈለገው ለማድረግ ዕድል በማግኘቱ ነው። ስለሆነም የዛሬው የኦሮምያ ክልልና የቤኔሻጉል „አስተዳዳሪዎች“ የምትሰሩት ስራ ሁሉ የውጭ ኃይሎችን ለማስደሰትና የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ እንዳያገኝና እፎይ ብሎ እንዳይኖር ነው። ይህ የማይገባችሁ ከሆነ በአንዳች ኃይል የምትወገዱበትና ፍርዳችሁን የምታገኙበት ቀን ይመጣል። ስራችሁን ሁሉ ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠርና የሚታዘብ ኃይል አለ። በታሪክ ውስጥ ህዝብን ሲያሰቃይና ሲገድል የኖረ አገዛዝ ሳይዋረድ የተባረረበት ጊዜ የለም። ለተወሰኑ ዓመታት አምባገነናዊና ፋሺሽታዊ አገዛዞች ቢዘባነኑም፣ ህዝባቸውንም ቢያሰቃዩና ቢጨፈጭፉም ሳይዋረዱ ስልጣናቸውን የለቀቁበት ጊዜ በታሪክ ውስጥ አልተመዘገበም። ሁሉም አንድ ቀን በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ወይም ፍርዱን የሚያገኝበት ቀን መምጣቱ አይቀርም። ይህም የታሪክ ግዴታ ነው።

                             የጥቁርና የነጭ ጁንታ ጉዳይ!

የጥቁር ጁንታ የሚባለውን አነጋገር ላይ በሳይንሳዊ መልክ ለማስረዳት የሞከርኩ ቢሆንም አንዳንድ ነገሮችን ማብራራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የጥቁር ጁንታ የሚለው አባባል ለወያኔ ብቻ የሚሰጥ አባባል መሆን የለበትም። የወያኔው ቅጥ ያጣና ከንቃተ-ሁሊና መጉደል ወይም መንፈሰ-አልባ ከመሆን ጋር የተያያዘ ቢሆንም እኛም ትንሽ እናስባለን የምንል ሰዎች በአጻጻፋችን፣ በአነጋገራችንና በአኗኗራችን፣ እንዲሁም ደግሞ በድርጊታችን በመሰረቱ ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ነው ስንሰራ የከረምነውና አሁንም የምንሰራው። አብዛኛዎቻችን በእነሱ ጥገኛ የሆንና፣ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ስም ባንጠለጠሉ ኢምፔሪያሊስታዊ ኢንስቲቱሽኖች ስር ተቀጥረን ስንሰራ የነበርንና አሁንም የምንሰራ በመሆናችን አገራዊና ብሄራዊ ስሜት የለንም። አንዳንዶቻችን ብንጽፍና ለአገራችን እንታገላለን ብንልም፣ ጽሁፎቻችንና አነጋገሮቻችን ስልትን የሚከተሉ፣ በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን በግልጽ የማያሳዩ፣ የጠላትን የተወሳሰበ ሴራና አካሄድ በደንብ የማያመላክቱ፣ የዕውነተኛውን የነፃነትና የዲሞክራሲ እንዲሁም ሳይንሳዊ የሆነውን የዕድገት ፈለግ የማያሳዩ ናቸው። አብዛኛዎቻችን በሶፊስታዊ ወይም ደግሞ ኤምፔሪሲዝም ተብሎ በሚጠራው ዕውነትን ከውሸት ነጥለን እንዳናይ በሚያደርግ የትምህርት ዘርፍ የሰለጠን በመሆናችን ለአገራችንና ለህዝባችን ሳይሆን ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ነው የምናደላው።

ስለሆነም ነው አገራችን ብዙ ሀብትና ለስራ የተዘጋጀ የሰው ኃይል ቢኖራትም ህዝባችን ባለፉት ሰባ ዓመታት ዕውነተኛውን የዕድገትና የሰላም፣ የነፃነትና የዲሚክራሲ ብርሃንን ማየት ያልቻለው። ይህ ጉዳይ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ያለ ችግር በመሆኑ ዛሬ በጥሩ አስተዳደር ጉድለት የሚታሙ አገሮች በሙሉ ያለባቸው ችግር ስልጣንን የሚቀዳጁና ፖሊሲን የሚያረቁ ኃይሎች በብዙ ሺህ ድሮች ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር የተቆላለፉ በመሆናቸው ነው። በተለይም ከከፍተኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚወለዱ አስራሁለተኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ በቀጥታ የሚላኩት ሀርቫርድና ቺካጎ የመሳሰሉ የኤሊቶች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነው። አብዛኛዎች ለስልጣን የሚበቁትም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰለጠኑ በመሆናቸው የሚያወጡት ፖሊሲ ወደ ውስጥ ያተኮረና ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ግንባታ የሚያመጣ ሳይሆን በተለያዩ መሳሪያዎች ሀብት ወደ ውጭ እንዲፈስ የሚያደርግ ነው ማለት ይቻላል። ኢምፔሪካል ጥናቶችም ይህንን ነው የሚያረጋግጡት።

ወደ መንግስት መኪናም ስንመጣም ይህንን ነው የምንመለከተው። የአገራችንም ሆነ የተቀሩት የአፍሪካና የሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የመንግስት መኪናዎች፣ ማለትም የወታደሩ፣ የፀጥታ ኃይሉ፣ የፖሊስና የሲቪል ቢሮክራሲው ከታች ወደ ላይ ከየአገሮች ፍላጎትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር እየተነፃፀሩ የተገነቡ ባለመሆናቸው የግዴታ አምባገነናዊ ባህርይነት ያጠቃቸዋል። ተግባራቸውም አንድ ህዝብ ነፃነት እንዳይሰማውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዳይዳብር ማድረግ ነው። ዝብርቅርቅና ውዥንብር ሁኔታዎችን በመፍጠር በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረውን ህዝባቸውን እየተሰቃየና እየተሰደደ እንዲኖር ማድረግ ነው። ስልጣንን የተቆናጥጠው የውስጥ ኃይል የውጭው ኃይል ታዛዥ በመሆን ዕውነተኛ ዕድገትና ዲሞክራሲ እንዳይዳብሩ ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ የረቀቀና ብሄራዊ ስሜት የሌለው መንግስታዊ አደረጃጀትና ዕውነተኛ የሆነ ህዝባዊ ሀብትን የማይፈጥር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአብዛኛዎቻችን በግልጽ የሚታዩ አይደሉም። በተለያዩ የኢኮኖሚክስ ዕውቀቶች መሀከል ያለውን ልዩነት፣ ማለትም በፊዩዞካራቲክስ፣ በመርከንታሊዝም፣ በክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ በማርክሲስት ኢኮኖሚክስ፣ በኒዎ-ክላሲካልና በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ፣ በኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስና፣ በፊዚክስና በባዮሎጂ ላይ በተመሰረተው ፊዚካል ኢኮኖሚክስ ሳይንስ ተብለው በሚጠሩት የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ዘርፎች መሀከል ያሉትን ልዩነቶች ስለማንገነዘብ ካለምንም ምርምርና ክርክር በጭፍን እየተመራን ተግባራዊ የምናደርጋቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ድህነትን ከመፈልፍ በስተቀር የተስተካከለ ዕድገትን ለማምጣት አልቻሉም። ይህንን የሚረዱ የውጭ ኤክስፐርቶችና የዓለም ኩሙኒቲው በመባል የሚታወቁት ግፊት እያደረጉብን ከፍተኛ መቀመቅ ውስጥና የእርስ በርስ ሽኩቻ ውስጥ ሊከቱን ችለዋል። ስለሆነም የዲግሪ እንጂ ሁላችንም በጥቁር ጁንታ ውስጥ የምንካተትና የመጨረሻ መጨረሻ አገራዊ ውድመትን የምናመጣና ህዝባችንም እንዲበታተን የምናደርግ ነን።

ወደ ነጭ ጁንታው ስንመጣት፣ ይህ ኃይል የበላይነቱን ላለማጣት ሲል በከፍተኛ ደረጃ የሚፍጨረጨርና አንዳንድ አገሮች ከቁጥጥሩ ስር የሚውጡ ከመሰለው አክራሪ ኃይሎችን በማስታጠቅና ሽብርተኝነት እንዲካሄድ በማድረግ በአንድ አገር ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር እርኩስ ስራ የሚሰራ ነው። በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ቢኖረውም በስግብግበነት መንፈስ እየተመራ በሁሉም አገሮች ላይ የበላይነቱን ያሰፈነና የሚያሰፍን፣ እንዲሁም የብዙ ቢሊዮን ህዝቦችን ዕድል የሚወስንና የሚቆጣጠር ነው። በአብዛኛዎች የካፒታሊስ አገሮች ውስጥ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስም ስልጣንን የተቆናጠጡና የህዝብ ተጠሪዎች የሚባሉት በተጨባጭ ሲታይ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ አይደሉም። የስለላ ድርጅቶችና ውስጥ ለውስጥ የተደራጁ ምስጢራዊ ኃይሎች ናቸው ስርዓቱን የሚቆጣጠሩት ማለት ይቻላል። የእነዚህ ሁሉ ተግባር ህገ-መንግስትን በመጠበቅ ሽፋን ስም የተደራጁ ቢሆኑም፣ ወደ ውጭ ደግሞ ለየመንግስታቱ የሚሆን የማይሆን የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ በዚህ ረገድ የውጭ ፖሊሲ እንዲረቅ የሚያደርጉ ናቸው። ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና በአሜሪካንም ጭምር በዲሞክራሲ ስም ስልጣንን የጨበጡ የተለያየ ስም ያላቸው ፓርቲዎች በመሰረቱ የትላልቅ ኩባንያዎችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። በአፍሪካና በተለያዩ የአረብ አገሮች፣ ኢራክ፣ ሊቢያ፣ ሲሪያ፣ በተጨማሪም በአፍጋኒስታን አክራሪ የእስልምና ተከታዮችን ለመዋጋት በሚል ስም የሚካሄደው ጦርነት ታሪክና ባህል የነበራቸውን አገሮች በታትኖ በእነሱ ቁጥጥር ስር ማምጣትና የጥሬ ሀብታቸውን ለመቆጣጠር የሚደረግ ዐይን ያወጣ ወረራ ነው።

ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ምድር የሚካሄደው ጦርነትና አገራችንን መክበብና ማዋከብ ከዚህ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።  በዚህ ዐይነቱ ከበባና ጦርነት ውስጥ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ግብጽና ሱዳን እጅና ጓንቲ ሆነው በመስራት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከተውናል። ይህንን ዐይነቱን ከበባና ጦርነት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያስተናግደውና አገራችንም እንድትበታተን የሚያደርገው ለጥቅሙ የተገዛ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው የተውጣጣ የልዩ ልዩ ብሄረሰብ ኤሊት ነው። አገዛዙም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የውስጥ ኃይል እንዲሰባሰብና በጋራ እንዲታገል ከማድረግ ይልቅ አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ በመጫወት እንድንዘናጋ በማድረግ ላይ ነው። በተለይም በአካባቢው የተሰባሰቡት የፖለቲካ አማካሪዎችና የዎል ስትሪትን ጥቅም የሚያስጠብቁና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎችም አገራችንን ከመበታተን የሚያድኑ ሳይሆኑ መበታተኗን የሚያፋጥኑ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ብሄራዊ ስሜት የሌላቸው፣ ሞራላዊ ብቃትነትን በጭንቅላታቸው ውስጥ ያልቀረጹ፣ ባህልና ታሪክ ምን እንደሆኑ ያልገባቸው፣ ለራሳቸውና በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ እንጂ ለህዝብና ለተከታታዩ ትውልድ የሚያስቡ አይደሉም። ስራቸው በሙሉ ለነጩ ጁንታ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የወንድማችን የአቶ አባንግ የመሰባሰብና የጋራ ጥሪ መልዕክት ትክክክል ቢሆንም የሃሳብና የአመለካከት፣ እንዲሁም ደግሞ የአገር ወዳድ ስሜት እስከሌለን ድረስ በአንድ የአስተሳሰብ ክልል ዙሪያ ልንመጣ አንችልም። እንደ ትላንትናው ዛሬም የፖለቲካ ሜዳውን የተቆጣጠሩት ኃይሎች በህዝባቸው ላይ ዕምነት ያላቸው አይደሉም። በጭንቅላታቸው ውስጥ አንድ ፕሮግራምድ የሆነ ነገር ስላለ ከፀረ-ዕድገትና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በፍጹም ሊላቀቁ አይችሉም። የፖለቲካ ባዮግራፊያቸውና አጻጻፋቸው እንደሚያረጋግጠው መንፈሳቸው ተሃድሶን ያገኘ አይደለም። ርዕያቸው ጥበብና ሳይንስን እንዲሁም ቴክኖሎጂን ያስቀደመ አይደለም።  እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ፣ ባንዲራዬ ባንዲራዬ እያሉ ቢጮሁም የጠራ ሃሳብና አመለካከት የላቸውም። የሚያወሩትና የሚጽፉትም በሳይንስና በፍልስፍና ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ ስለምን እንደሚያወሩ ግልጽ አይደለም። ዛሬ በመሀካለችን ያለው ልዩነት በግራና በቀኝ መሀከል ባለ አመለካከት የሚሳበብ ሳይሆን፣ የአገራችንና የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ሁኔታ በትክክለኛው መነጽር በማንበብና ባለማንበብ መሀከል ነው። ስለሆነም የመሰባሰቡ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው። በእኔ ዕምነት የፖለቲካውን መድረክ ለመቆጣጠር የሚችሉ በትክክለኛ አመለካከት የሚመሩ ሁኔታውን መቆጣጠር አለባቸው። ደፋር መሆን አለባቸው። ከፊዩዳላዊ አስተሳሰብና ከይሉኝታ መላቀቅ አለባቸው። ለዕውነተኛ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መረጋገጥ የሚደረግ የፖለቲካ ትግል ከይሉኝታ መላቀቅ አለበት። ባጭሩ ትግሉ ሳይንስንና ፍልስፍና የተከተለ፣ ያሉትን ችግሮች በግልጽና በቀላል ቋንቋ የሚያስቀምጥና አመራርም የሚሰጥ መሆን አለበት። ማንኛውንም ዐይነት የጽንፈኝነትና የካድሬ ፖለቲካን የሚዋጋና፣ የጠራ ሃሳብንና የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድም መሆን አለበት። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                                     fekadubekele@gmx.de

 

ጥልቅ ለሆነ አስተሳሰብ የሚከተለውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ። www.fekadubekele.com

https://www.youtube.com/watch?v=lgQ-ykPQZds

 ለማዘን፣ ለመሳቅና የመጨረሻ መጨረሻም ለመደሰት ይህንን ግሩም ፊልም ተመልከቱ።

https://www.youtube.com/watch?v=ETxeUEKJ8vQ