[gtranslate]

 ፖለቲካ እንደ ዕምነትና እንደ መርህ ከመታየቱ በፊት መቅደም የሚገባቸው ነገሮች!

         -የመንፈስ ነፃነትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በትክክል የማንበብ አስፈላጊነት! II

                                                                                             

                                                                        ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                       ህዳር 11፣ 2019

መግቢያ

አብዮቱ ከፈነዳና ብዙ ትርምስ ከተፈጠረ በኋላ ደጋግሞ የሚነሳው ጥያቄና ክርክር አገራችን እንደዚህ ዐይነት ምስቅልቅል ውስጥ ልትገባ የቻለችው ከታሪካችንና ከአስተሳሰባችን ጋር ሊጣጣም የማይችል ርዕዮተ-ዓለም በማስገባታችን ነው የሚል ነው። በሌላ ወገን ማርክሲዝም ሌኒንዝም  ከመግባቱ በፊት ከባህላችን ጋር „የማይጣጣሙ“  አስተሳሰቦችና የአኗኗር ስልቶች  በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አገራችን ውስጥ ሰተት ብለው በመግባት የህይወታችን አካል ለመሆን በቅተዋል። እራሳችን ያልፈጠርናቸው አያሌ ነገሮች በመግባት እንድንጠቀምባቸው ተደርጓል። ጥያቄው የውጭ ርዕዮተ-ዓለምን መዋሱ ላይ ሳይሆን እንዴት እንጠቀምበታለን ነው። በትክክል ገብቶናል ወይ? በማርክሲዝም ሌኒንዝም ቲዎሪ አማካይነት የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር ማጥናትና ማወቅ ይቻላል ወይ? በጊዜው ይታይ የነበረውን ድህነት፣ የስራ-አጥነትና ረሃብ ምክንያቶችን ለማወቅ ማርክሲዝምንና ሌኒንዝምን እንደመመርመሪያ መሳሪያ ሊያገለግሉን ይችላሉ ወይ?  ባጭሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ሁኔታ በቲዎሪው አማካይነት ማወቅ ይቻላል ወይ? በተጨማሪም የማርክስና የሌኒን ቲዎሪዎች አገራችንን ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ያስችሉናል ወይ? እነዚህንና ሌሎች አያሌ ጥያቄዎችን ያቀረብን እንደሆን ብቻ ሚዛናዊ ፍርድ ለመሰጠት እንችል ይሆናል።

ለማንኛውም በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረውን አሳዛኝ ሁኔታ አስመልክቶ የሚወነጀለው የተማሪው እንቅስቃሴና ኮሙኒዝምን ተግባራዊ አደርጋለሁ“ ብሎ የተነሳውን የደርግን አገዛዝ ነው። ይሁንና ግን ዛሬ አገራችንና ህዝባችን ለገቡበት ፈታኝ ሁኔታ ተጠያቂው የማርክሲዝምና የሌኒንዝም ቲዎሪ ለመሆኑ በቴዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ የተረጋገጠ ነገር የለም፤ በጊዜው በአብዮቱ ውስጥ የተሳተፉትና አሁንም በህይወት የሚገኙ አንዳንድ መሪዎች ማርክሲዝምን-ሌኒንዝምን ተጠያቂ ሲያደርጉ አልተሰማም። አብዮቱ ለምን እንደዚህ ዐይነት ምስቅልቅል ሁኔታዎችን አስከተለ? ለምንስ ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ ተደረገ?  ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምክንያት ሲሰጡ አልተሰማም። ይሁንና የቀድሞ የኢህአፓ አባል የነበረው፣ በኋላ የብአዴን አባል አመራር የነበረውና ከነመለስ ዜናዊ ጋር ስልጣን ላይ የወጣው ታምራት ላይኔ „ማርክሲዝም ሌኒንዝም አሳስቶት“  እንደዚያ ዐይነቱን ወንጀል እንደፈጸመ እየደጋገመ ነግሮናል።

በእርግጥ በአብዮት ስምና በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስም እንደዚያ ዐይነት ውርጅብኝና ግድያ ሲፈጸም በጊዜው ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ ሰዎች፣ ወይም ደግሞ የዘመድ አዝማድ የተገደለባቸውን ሰዎች ዋናው ምክንያት ማርክሲዝም ሌኒንዝም አይደለም ብሎ ማሳመን በፍጹም አይቻልም። ማንኛውም ሰው ፍርድ የሚሰጠው ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎችን አስተሳሰብ በመመርመር፣ ያደጉበትን ህብረተሰባዊ ሁኔታ በማጥናት፣ እንደዚህ ዐይነቱ ርዕዮተ-ዓለም ከመግባቱ በፊት የአብዮቱ ተዋንያን የተኮተኮቱበትን ርዕዮተ-ዓለም በመመርመር አይደለም። ከዚህም በላይ ፍርድ በጅምላ ሲሰጥ ማን በመጀመሪያ ደረጃ ተኩስ እንደከፈተና፣ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ ለማድረግ እንደበቃ በፍጹም የሚጠይቅ የለም። ከዚህም ባሻገር በአብዮቱ ውስጥ የተደረገው ትንቅንቅ በውስጥ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችም እጃቸው እንዳለበትና፣ በቀይና በነጭ ሽብር ውስጥ የማይናቅ እርኩስ ሚና እንደተጫወቱ ሊያወጣና ሊያወርድ የሚሞክር ሰው በፍጹም የለም። ኮሙኒዝምን ወይም ደግሞ የማርክሲዝምን ሌኒንዝም ርዕዮተ-ዓለም በጭፍን የሚጠላው ሰው ተጠያቂ የሚያደርገው ይህንኑ ርዕዮተ-ዓለም ነው። ይሁንና ግን ተደጋግሞ የሚዘነጋ ጉዳይ አለ። በመጀመሪያ ደረጃ የጊዜ ጉዳይ(Timing) አለ። ይህም ማለት አብዮቱ ሲፈነዳ ጊዜው አመቺ የሆነውን ያህል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ኢምፔሪያሊዝምና ሌሎች አጎራባች አገሮች እንደዚህ ዐይነቱን መሰረታዊ ለውጥ አጥብቀው ለመዋጋት የሚያስችላቸው ኃይልና፣ ይህንን ፍላጎታቸውንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚችል የውስጥ ኃይል እንደነበረ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ አብዮቱ የፈነዳው በግብታዊ መንግድ ወይም ሳይታሰብ በመሆኑ የተሰበጣጠረውንና „የተለያየ ዓላማ“ የነበረውን ኃይል በአንድ መሰረተ-ሃሳብ ዙሪያ በማሰባሰብ እንዲታገልና አገር ለመገንባት እንዲነሳ ማድረግ በፍጹም አይቻልም ነበር። በሶስተኛ ደረጃ፣ የህዝቡ አስተሳሰብና፣ በተለይም ደግሞ የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ይህንን ርዕዮተ-ዓለም የመቀበልና የአገር መገንቢያ መመሪያ የማድረግ አቅም አልነበረውም። የአገራችን የማቴሪያል ወይም ደግሞ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግኑኝነት በጣም ደካማ ስለነበር የነቃና ለውጥን የሚፈልግ ኃይል ሊፈጥር አልቻልም። ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በቆራጥነትና በተከታታይነት በአብዮቱ ጎራ ሊሰለፍ የሚችል ኃይል ማፍራት በፍጹም አይቻልም ነበር። በአራተኛ ደረጃ፣ ተራማጅ ነኝ በሚለው ሰፈር የተፈጠረው የእርስ በእርስ ሹከቻና ጥላቻ አብዮቱን አደጋ ውስጥ መጣሉ ብቻ ሳይሆን ተተኪ የማይገኝላቸውን በጊዜው ተማሩ የሚባሉ ምሁሮች እንዲያልቁ ተደረገ። በተጨማሪም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብና ወጣት አለቀ። አብዛኛው በማያውቀው መንገድ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ አባል በመሆን የእሳት እራት ሊሆን በቃ። በአምስተኛ ደረጃ፣ ካለምንም ሳይንሳዊ ጥናትና ካለበቂ ኢምፔሪካል መረጃ „አብዮት ሊሳካ የሚችለው ደም በማፍሰስ ብቻ ነው“  የሚለው  አስተሳሰብ በብዛት ስለተስፋፋ፣ በተለይም በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ሳይኖረው አብዮቱ ውስጥ የተቀላቀለውና አልፎ አልፎም ብሶት የነበረው አጋጣሚ አገኘሁ በማለት በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ እንደዚህ ዐይነቱን አሰቃቂ ድርጊት እንዲፈጽም አደረገው። ባጭሩ አብዮቱ የቂም በቀል መወጣጫ ጊዜም ሊሆን በቃ።

ከዚህ ስንነሳ መጠየቅ ያለብን ጉዳይ እንዲያው በቁንጽልና ፊት ለፊት የሚታየውን ነገር እንደዋና ምክንያት አድርገን በመውሰድ ሳይሆን ከዚህ ባሻገር ያሉትን ምክንያቶች በመመርመር ነው። በተለይም አሁን በቅርቡ የቀድሞ የመኢሶን መሪ የነበረውን የአቶ አንዳርጋቸው አሰግድን የቃለ-መጠይቅ ምልልስ ከተመለከትኩኝና ካዳመጥኩኝ በኋላ ጠያቂው አቶ ደረጀ ኃይሌ በደርግ ወታደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉትንና ያቀረባቸውን የአብዮቱ ተዋንያንን ፎቶዎች ስመለከት ነገሩ እንደዚህ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ጠለቅ ብለን በመሄድ በተለይም በአብዮቱ ውስጥ የተሳተፈውንና በእልቂት ውስጥ ዋና አቀነባባሪ የሆኑትን ሰዎች ስነ-ልቦና መመርመር ያለብን ይመስለኛል። አሁንም በሌላ አነጋገር መጠየቅና መመርመር ያለብን ጉዳይ አንድን ርዕዮተ-ዓለም በጭፍን ከመወንጀል ይልቅ የራሳችንን ስነ-ልቦናና እንደዚህ ዐይነቱን ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ወይም አብዮት ካለደም መፋሰስና ሳንወነጃጀል ማስተናገድ እንችላለን ወይ? ብለን ነው መጠየቅ ያለብን። በእኔ ዕምነት አንችልም የሚል ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት መንፈሳችን ለዚህ የተዘጋጀ አልነበረም፤ በአንድ አስተሳሰብ ዙሪያ በመሰባሰብ ለአንድ ዓላማ የመታገል ሞራላዊ ብቃት አልነበረንም የሚል ነው። ዞሮ ዞሮ ባህርያችን በጣም አስቸጋሪ ነው ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ፖለቲካን እንደ ዓላማ ወይንም የመታገያ መሳሪያ አድርገን ከመውሰዳችን በፊት መጓዝ ያለብንን ክንውናዊ ሂደት የተረዳን አልነበርንም። በሌላ አነጋገር ካለመንፈሳዊ አብዮት በፊት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ ማምጣት በፍጹም አይቻልም። ይህም ማለት የግዴታ መንፈስን ከማንኛውም እቡይ ተግባር ማጽዳት ያስፈልጋል። የህብረተሰብን ጥያቄ በአርቆ-አስተዋይነት መነፅር በበቂው ማጥናትና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል።  በተለይም በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የሚታየውን አደገኛ ሁኔታ ለመወጣትና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምንፈልግ ከሆነ ከመንፈስ አብዮትና ጠለቅ ካለ ምሁራዊ ዝግጅት ውጭ ሌላ አማራጭ ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም።

 የመንፈስ ነፃነት አስፈላጊነት!

በዚህ መሰረታዊ ሃሳብ ላይ ሀተታ ከመስጠቴ በፊት እንደገና ስለ አብዮቱ አንዳንድ ነገሮችን ላትት። አንዳንዶች ይህ ያለፈበት ነገር ነው፤ ለምንድነው  እየደጋገምን እዚያው ላይ የምንጽፈው? ትሉ ይሆናል። እዚህ ላይ ስለአብዮቱ ግሩምነት ወይም ደግሞ ሰለተሰራው አሰቃቂ ድርጊት ለማተት ሳይሆን፣ በዚያን ጊዜ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላምና ስልጣንን እስኪለቅ ድረስ በሌላ መልክ መቀጠሉን ለማሳሰብ ነው። በዚህም በዚያም ብለው ስልጣንን የሚቀዳጁ ኃይሎች ስልጣን ላይ ለመቆየትና የፈለጉትን ነገር ለማድረግ ሲሉ ሰውን ከመግደልና ከማሰቃየት ሌላ የሚታያቸው ነገር እንደሌለና፣ በብዙዎቻችንም ዘንድ ይህን ዐይነቱን አሰቃቂ ድርጊት እንደተራ ወይም እንደኖርማል ነገር አድርጎ የመውሰድ ባህል የተስፋፋ መሆኑን ለማሳሰብ ነው። በተለይም አንዳንዶቻችን  ካለምንም ፀፀት ከድርጊቱ ፈጻሚዎች ጋር ስንሳሳቅ፣ ስንበላና ስንጠጣ ስመለከት በምን ዐይነት የሞራል ውድቀት ውስጥ እንደምንገኝ ለማሳየት ነው። „ለውጥ መጣ፣ በለውጥ ዓለም ውስጥ ነው የምንገኝው“  ከተባለም ወዲህ ዛሬም  በሰላም ኖቭል ተሸላሚው ዘመን ይህ ዐይነቱ አሰቃቂ ድርጊት እንደባህል ሆኖ በመቀጠል ብዙዎቻችንን ይህን ያህልም የሚያሳስበን ጉዳይ አይደለም። በተለይም ሰላም የሰፈነ ይመስል ስንትና ስንት ሰው በጽንፈኛ ኃይሎች ሲገደል፣ አንዳንዶች ደግሞ ካለምንም ወንጀል እስር ቤት ሲወረወሩ በዚህ ዐይነቱ ቀውጢ ወቅት ለምርጫ እንወዳደር ማለት ወይንም ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ የደስታ ጋጋታ ማንጋጋት የቱን ያህል አረመኔዎች እንደሆን ነው የሚያረጋግጠው። ስለሆነም በአብዮቱ ዘመን የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ባለፉት 27 ዓመታትና ዛሬ ደግሞ በልማትና በብልጽግና ስም አሁንም ህዝባችን ፍዳውን ያያል፤ አገር ትታመሳለች፤ ጥቂቶች ጊዜ መጣልን ብለው ይፈነጫሉ፤ የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፍቷቸዋል፤ በስልጣን ተሳክረዋል።

ከዚህ ስንነሳ አሁንም እንደገና ወደ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ የቃለ-ጥያቄ ምልልስ ጋ ስመጣና፣ ጋዜጠኛው በተለይም የመኢሶን ታጋይ የነበረውን እጅግ በሚያሳዝን መንገድ የተያዘውንና ዐይኑ እየተጎለጎለ በመውጣት የተገደለውን የአቶ መስፍን ካሱን ሁኔታ ሲናገር ኢትዮጵያኖች እስከዚህ ድረስ አረመኔዎች ነን ወይ? ብዬ ስጠይቅ የማገኘው መልስ በተለይም ንዑስ ከበርቴው አረመኒያዊ ባህርይ እንዳለው ነው የምረዳው። በአብዮቱ ወቅት እንደዚህ ዐይነቱ ድርጊት የተደጋገመና በራሳቸውም የማርክሲስት ድርጅት ነን በሚሉ አንዳንድ ድርጅቶችም ውስጥ አንዳንድ አባሎች የፓርቲው መሪዎች አካሄድ ያላማራቸው ጥያቄ ሲጠይቁና አማራጭ መንገድ ሲያመልክቱ እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልክ ሊገደሉ በቅተዋል። ይሁንና ዛሬ በህይወት የሚገኙ የዚህ ዐይነቱ አሰቃቅ ድርጊት አቀነባባሪዎች አንድም ቦታ ላይ ለድርጊታቸው በመጸጸት ይቅርታ ሲጠይቁ አልሰማሁም። እንዲያውም አላውቅም፤ በቦታው አልነበርኩም በማለት ነበር እጅግ አሳፋሪ መልስ የሚሰጡት። እነዚህ የተለያዩ ድርጅት መሪዎች ልክ የጀግንነት ስራ የፈጸሙ ይመስል ጋዜጠኛ ነን በሚሉና ኃላፊነት በጎደላቸው በተደጋጋሚ ቃለ-መጠይቅ ሲጠየቁ ስሰማ ሁላችንም የቱን ያህል የሞራል ውድቀት ውስጥ እንደምንገኝ ነው የሚሰማኝ። ስለሆነም ወደፊት ማንም የማይገደልበት፣ ካለምንም ወንጀል የማይታሰርበት፣ በፖሊስ ግልምጫና ድብደባ የማይካሄድባት አገር ለማየት ከፈለግን የግዴታ የድሮ አሰቃቂ ድርጊቶችን ማንሳት በጣም አሰፈላጊ ይመስለኛል። ይህንን እየመላለስን ካልጠየቅንና መልስም ለመስጠት የማንችል ከሆነ ህዝባችን የዝንተ-ዓለሙን ፍዳውን እያየ እንዲኖር ነው የምናደርገው። ያም ሆነ ይህ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ የሰጠው የቃለ-መጠይቅ ምልልስ በእኔ ዕምነት ሚዛናዊና የበሰለ መልስ ነው ብዬ እገምታለሁ። ይህ ዐይነቱ ግምት የእኔ ብቻ ሳይሆን የጠየቅኋቸው ሰዎች በሙሉ ተመሳሳይ ግምት እንዳላቸው ገልጸውልኛል።

ለማንኛውም በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የተደረገውን ትግል ለተመለከተ መንፈስን ከማጽዳት በፊት ወይንም እራስን እየደጋገሙ ከመጠየቅ በፊት በፖለቲካ ስም የሚካሄድ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ አንድን አገር በቀላሉ ልትወጣ የማትችለው ማጥ ውስጥ ነው የሚከታት። ወደድንም ጠላንም  የሰውን ልጅ  ዕድል ወሳኞች እራሱ አንድ ህዝብ ሳይሆን አንድ ተማርኩ ነኝ የሚል ኃይል እንደመሆኑ መጠን ይህ ዐይነቱ ኃይል በቂ ምሁራዊ ዝግጅትና የጭንቅላት የጽዳት ዘመቻ ከማካሄዱ በፊት ተግባራዊ አደርጋለሁ የሚለው ፖለቲካ ወደ ብልጽግናና ወደ መረጋጋት የሚያመራ ሳይሆን ወደ ትርምስና ወደ ኋላ-ቀርነት ነው። በተለይም ብዙ ነገሮች ተጣመው በሚቀርቡበት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ተጨቁነን ነበር የሚሉ፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ ተወካይና ነፃ አውጭ ነን በማለት እራሳቸውን የሾሙ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች አጋጣሚውን በማግኘት የበላይነትን ለመቀዳጀት እንጂ ወገናችን ነው የሚሉትን ነፃ ለማውጣት አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የዚህ ወይም የዚያ ተወካይ ነኝ የሚል የብሄረሰብ ኤሊት ባለፈው 27 ዐመታት እንዳየነው የራሱን ጥቅም ብቻ ነው  የሚያስጠብቀው። በተለይም የኦሮሞ ክልል ወደ ኋላ ከቀሩት ክልሎች ውስጥ አንዱ አካባቢ ሲሆን የኦሮሞ ወጣት ሴቶች አበባ ተካይ እንዲሆኑ ነው የተደረጉት። አሁን ደግሞ አዲስ በተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተቀጥረው በመስራት በከፍተኛ ደረጃ እየተበዘበዙ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ቂም በቀልን ከማስቀደም በስተቀር እወክልሃለሁ የሚሉትን ብሄረሰብ  የማሰብ ኃይሉን ከፍ ለማድረግና ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ የወሰዱትና የሚወስዱት የማስተማር እርምጃ የለም። ሰሞኑን እንዳየነው ምንም ዕውቀትና  ስራ የሌለው የቄሮ ወጣቶች ነኝ የሚሉ በጅምላ በመነሳት በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ የሚኖሩ ንፁህ ዜጋዎችን ገድለዋል። ብዙ ንብረትም አውድመዋል። የአንድ ነፃ አውጭ ኤሊት ወይም የአንድ ክልል አመራር ተቀዳሚ ተግባር ለኗሪው ዜጋ፣ በተለይም ለወጣቱ የሙያ ስልጠና መስጠትና የስራ-መስክ መክፈት ነው። ይህንን ከማድረግ ግን የየክልሉ መሪዎችና፣ በተለይም የቄሮ ወጣቶች መሪ ነኝ የሚለው ጃዋር ምንም የማያውቀውን ወጣት በስሜት በመንዳትና በወገኑ ላይ እንዲነሳ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የታሪክ ወንጀል እየፈጸሙ ናቸው። ጩኸታቸውና ድርጊታቸው በሙሉ ዓላማ የሌለው ነው።

ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያ ምድር በነፃ አውጭነት ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶችና ትላንትም ሆነ ዛሬ ስልጣንን የተቀዳጁ እንደምናየው አገርን ከመገንባት ይልቅ የኋሊት ጉዞ የሚያስኬድ „ባህል“ እየቆፈሩ በማውጣት ኋላ-ቀርነትና ድህነት ስር እንዲሰዱ በማድረግ ላይ ናቸው። ሰሞኑን የተከበረው „የኢሬቻ በዓል“ የሚያረጋግጠው ይህንን ነው። የበላይነትን ማረጋገጫና ማወጃ(Macht Demonstration= Demonstration of Power) የሆነና፣ የአንዳንድ ኦሮሞ ኤሊቶችን ባዶ ጭንቅላትነት ያረጋገጠ ነው። ማሰብ የማይችሉና ይህ ዐይነቱ የበላይነትን ማረጋገጫ አከባበር አንድ ቦታ ላይ ቡን ብሎ እንደሚበተን ግልጽ የሆነላቸው አይመስለኝም።

የዚህ ዐይነቱ የበላይነትን ማረጋገጫ አከባበርም ሆነ በወያኔ ዘመን የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊትና አገርን አፍራሽ „ፖሊሲ“ ስንመለከት የየድርጅቶቹ መሪዎች ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ሁኔታና ህዝባችንና አገራችን የተጓዙበትን አስቸጋሪ ጉዞ የመረዳት ኃይላቸው እጅግ ደካማ እንደሆነ ነው። ባለፈው ጽሁፌ ላይና ቀደም ብዬ በተለያዩ ጊዜያት ባወጣኋቸው ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በቂ ምሁራዊ ዝግጅት ሳያደርጉና፣ በተለያዩ ምሁራን ዘንድ ክርክር ሳይደረግ በዝግ ችሎት ወይም በጦርነት ስልጣን ላይ መውጣት ለራስ ጥቅም ካልሆነ በስተቀር አንድን ህዝብ ነፃ ሊያወጣው በፍጹም አይችልም። የነፃ አውጭ እንቅስቃሴነት በተካሄደባቸው በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚታየው ይህ ሁኔታ ነው። በምሁራዊ መነፅር እየተመረመረና እየተገመገመ የማይካሄድ የጦር ትግል የመጨረሻ መጨረሻ አገርን ማዳከምና አንድ ህዝብ በእራሱ ላይ እንዳይተማመን መደረጉ ብቻ ሳይሆን የውጭ ኃይሎች መጥተው የአገርን እሴትና የተለያዩ ባህሎችን እንዲያፈርሱ የሚጋብዝ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። ይህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ጥበት የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ነን በሚሉ ድርጅቶች ውስጥ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በእራሳቸውም „ብሄራዊ ባህርይ አለን“ በሚሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮችም ውስጥ ያለ ችግር ነው። ባጭሩ በሁላችንም ዘንድ አንድን ነገር በጥልቀትና በሰፊው፣ እንዲሁም  ከተለያየ አቅጣጫ የመመርመር ችግር አለ። በተለይም በፖለቲካና በኢኮኖሚ ኤሊቱ ተደጋጋሚ ጥፋትም ሆነ ወንጀል፣ እንዲሁም የአገርን እሴት የሚያጠፋ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን ለምንድነው ፖሊሲው የማይቀየረው? ሌላስ አማራጭ የለም ወይ? ብሎ የሚጠይቅ ባህል በፍጹም የለም።

የዚህ ሁሉ ችግር አሁንም ቢሆን ሰፋ ያለ አስተሳሰብ እንዲኖረን ጥረት አለማድረግ ነው። በተራ ዕውቀት የአንድን ህብረተሰብ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ኃይል አለን ብለን ስለምንገምት ነው።  ካንት የሚባለው ፈለሳፋ መገለጽ ማለት ምን ማለት ነው?( What is Enlightenment?) በሚለው ጽሁፉ ውስጥ የሰው ልጅ በመሰረቱ ሰነፍ ነው ይላል። ዝም ብሎ በጭፍን ከመጓዝ በሰተቀር በጥልቀትና በስፋት ለመመራመር አይፈልግም ይላል። የነገሮችን አመጣጥ ለመረዳት ጥያቄ ለመጠየቅ አይሻም። እንዲያው ብቻ ዝም ብሎ በጭፍን መጓዝን ይመርጣል። ካንት በዚህ መልክ ያስቀመጠው አገላለጽ ወይም ጥያቄ የአገራችን ችግር ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች ውስጥ ያለና፣ በማዕከለኛው ዘመን የአውሮፓን ህዝብ ወደ ድህነት፣ የማያቋርጥ ጦርነትና በሽታ ውስጥ የከተተ ነው። ስለዚህም ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እስከ ማዕከለኛውና አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ፈላስፋዎች ሆን ብለው ቅድሚያ የሰጡት በጭንቅላት ላይ ከፍተኛና የማያቋርጥ ስራ መስራት የማሰብ ኃይልን ከፍ ማድረግ ሲችል፤  ከቂም-በቀል ነፃ የሆነ በተለይም ምሁራዊ ኃይልን ማፍራት ይቻላል የሚል ግምት አላቸው። ስለሆነም በስሜት ከመነዳት ይልቅ አርቆ-አሳቢነት በመቅደም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ችግሮች በፍትሃዊነት መነፅር የመታየትና መፍትሄ የማግኘትም ዕድል ያጋጥማቸዋል። ይህ ከመሆኑ በፊት በፖለቲካ ስም መነገድ በአንድ አገር ውስጥ ዘለዓለማዊ ትርምስ እንዲኖር ያደርጋል።

በጣም የሚገርመው ነገር ይህ ዐይነቱ ጭንቅላትን መነሻ አድርጎ ምርምር ማድረግ በግሪኩ ስልጣኔና በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተለመደ ሲሆን ለምን በእኛ አገር ውስጥ ይህ ዐይነት ባህል ሊፈጠር አልቻለም?  የመጀመሪያዎቹም ሆነ በኋላ የተነሱት የግሪክ ፈላስፋዎች ለምንስና እንዴትስ በጭንቅላትና በተፈጥሮ ላይ ምርምራቸውን እንዲያደርጉ አስገደዳቸው? ፍልስፍና ከተፈጠረና ከዳበረ ከሶስት ሺህ ዐመት በኋላ ለእኛ ይህ ጉዳይ ለምንስ አልተገለጸልንም? ለምንስ እየተንደፋደፍን እዚያው በዚያው በተመሳሳይ ነገሮች ላይ እንፋለጣለን?  እስከማውቀው ድረስ እስከዛሬ ድረስ አንድም ሰው ጥያቄ የጠየቀ የለም። አንዳንድ ሰዎች ነገሩ ታይቷቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ በነገሩ እንዳይገፋበት ቶሎ ብሎ ይዘጋል። አብዛኛዎቻችን በቁም ነገር ላይ ለመወያየት ፍላጎት አናሳይም። ስሜትን የሚነካና የሚቀሰቅስ ነገርን ብቻ ነው ለመስማት የምንፈልገው።  በጣም የሚያሳዝን ድርጊትና አስተሳሰብ በሁላችንም ዘንድ ተስፋፍቷል ማለት ነው። በቁም ነገር ላይ ከማውራትና ከመከራከር ይልቅ ሆን ብለን የያዝነው ነገር ተራ የሆኑ ነገሮችን እያነሳን መጨቃጨቅ ነው። የህዝባችንን ችግሮች የሚቀርፉ መሰረታዊ ጉዳዮችና ዕውቀት ላይ ከመከራከርና ከማጥናት ይልቅ ወደ ኋላ ተመልሰን ታሪካችን እንደዚህ ነበር ብለን ነው ለመዝናናት የምንሞክረው። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ወራሪነትና ወደ መቶ ዘመን ብቻ የለወጠው ታሪካችሁ እንደዚህ አይደለም፤ የሚያስተሳስረንም ታሪክ የለም በማለት የአገርንና የህብረተሰብን ጥያቄዎች እርግፍ አድርገን እንድንተው በማድረግ በማያስፈልጉ ነገሮች ላይ እንድንጨቃጨቅ ያስገድደናል።

ለማንኛውም አመንም አላመንም የግሪክ ፈላስፋዎች በአብዛኛው ጎኑ ፍልስፍናን የተማሩትና የኮረጁት ከጥቁር አፍርካ፣ በተለይም ከግብጽ ነው። ፕላቶንም ሆነ ፕይታጎራስ እንዲሁም ሶሎን ግብጽ አገር ለትምህርት እንደቆዩና ከቀሳውስቱ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንደነበራቸው የታወቀ ጉዳይ ነው። ይህ ጉዳይ የተረት ተረት ሳይሆን የተረጋገጠና በመጽሀፍ ተመዝግቦ ያለ ነገር ነው። የግሪክ ፈላስፋዎች ያደረጉት ነገር በጥቂት ምሁራን ዘንድ ይሽከረከር የነበረውን ዕውቀት ወይም ፍልስፍና ወደ ውጭ በማውጣት የማስተማሪያና የመከራከሪያ መሳሪያ ነው ያደረጉት። በዚህ መልክ ቀሰ በቀስም አዳዲስ ደቀ-መዝሙሮችን በማፍራት በጊዜው የነበረውን የዘልማድ አኗኗር መጋፈጥ ቻሉ። አስተሳሰብን በማሾል ለሚነሱ ችግሮች መልስ ለመመለስ ሙከራ ማድረግ ጀመሩ። ቀስ በቀስም የሳይንስን መሰረት ጣሉ። ባጭሩ በዚያን ጊዜም ሆነ በኋላ እንደዚህ ዐይነት ጭንቅላትን የሚያስጨንቅ ስራ ባይሰራ ኖሮ የሰው ልጅ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ በፍጹም ሊደርስ አይችልም  ነበር።

ይህ ዐይነቱ ጭንቅላትን የማስጨነቅና የማስገደድ ሁኔታ በካቶሊክ ኃይማኖት ትታመስ ወደ ነበረችው አውሮፓ በመሽጋገር ለእነ ዳንቴ፣ ኩዛኑስና ለሌሎች አያሌ ተመራማሪዎችና ፈላስፋዎች መመራመሪያ ዘዴ በመሆን ወደ ተግባርነት ሊለወጥ ቻለ። እነ ኮፐርኒከስ፣ ጋሊሊዮ፣ ኬፕለር፣ በሰዕልና በአርክቴክቸር ደግሞ፣ ሊዎናድርዶ ዳቪንቺ፣ ሚካኤል አንጀሎ፣ ራፋኤልና ብዙ የማቲማቲክስና የሳይንስ ሰዎች ብቅ ማለት ቻሉ። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት ወደ እንግሊዝ አገር በመሽጋገር እነ ኒውተን የመሳሰሉ ሰዎችን አፈራ። በፈረንሳይ ደግሞ እነ ሬኔ  ዴካና ቮልቴር የመሳሰሉ ፈላስፋዎችንና ሳይንቲስቶች ብቅ ማለት ጀመሩ።  ወደ ጀርመን አገር ስንመጣ ደግሞ ከኬፕለርና ከኩዛኑስ ባሻገር፣ እነ ላይብኒዝ፣ ካንትና  ሄገል፣ እንዲሁም ጎተና ሺለር፣ ሜንደልሰንና ሌሲንግ… ወዘተ. በመነሳት ዋናው ትግላቸውን በጭንቅላትና በምርምር ላይ አደረጉት። የመደብ ትግል ሳይሆን የጭንቅላት ስራና ምርምር ዋናው የነፃነት መሳሪያ መሆኑን አረጋገጡ።  በዕውቀት አማካይነትም የአንድን መደብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንዲሁም የርዕዮተ-ዓለም የበላይነት እንደሚያሸንፉ አረጋገጡ። ዕውቀትና ከዚህ የሚፈልቀው ኤስቴቲክስ ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገትና ስልጣኔ መመሪያ መሆኑን አመለከቱ። በሌላ አነጋገር በተሳሳተ መልክ የሚቀርበውንና የተወሰነውን ወይም ጠቅላላውን ማህበረሰብ ጭንቅላቱን ለማሳሳት(Manipulate) የሚራባ ትምህርትን መዋጋት የሚቻለው የመደብ ትግል እያሉ በመጮህ ሳይሆን የተሳሳተ ዕውቀት ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆነ ብቻ አወጁ። በተለይም ላይብኒዝ ለእንግሊዞቹ  የኢምፔሪሲስት ዕውቀት፣ ለእነ ጆን ሎክ የሰጠው አጥጋቢ ትንተና የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ባዶ(Tabula Rasa) ወረቀት ሆኖ እንዳልተፈጠረ የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ማንኛውም ዕውቀት ሊፈልቅ የሚችለው በጭንቅላት አማካይነትና ተፈጥሮንና ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትን በትክክል ማንበብ ሲቻል ብቻ  ነው። በዚህ መልክ የሚደረግ ትግል ዕውነተኛ ነፃነትን እንደሚያቀዳጅና በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም ስምምነትንና ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል አረጋገጠ።  ይሁንና የላይብኒዝና በኋላም የእነሺለርና ዊሊሄልም ሁምቦልድት አንድን መንግስት ጥበባዊ አድርጎ ማደራጀትና(The Aesthetic state) ለአንድ መደብ ብቻ እንዳያደላ ማድረግ በዘመነ ካፒታሊዝምና በግሎባላይዜሽን ዘመን ሊታሰብ የሚችል ነገር አይደለም። የካፒታሊዝም አይሎ መውጣት፣ ውስብስብ መሆንና የበላይነቱን ይዞ እንዲቆይ ለማድረግ በአፈ-ቀላጤዎቹ በየጊዜው የሚወጣው መንፈስን የሚሰልብ ወይም ሰፊው ህዝብ በፍጆታ አጠቃቀም ላይ ብቻ እንዲያተኩር የሚያደርግ ማስታወቂያና ቲዎሪ የሚመስል ቅስቀሳ መንግስትን ወገነ-አልባ ሊያደርገው በፍጹም አልቻለም። የካፒታሊዝም የማኒፑሌሽን ኃይል የተወሳሰበና ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ወደድንም ጠላንም መንግስት በካፒታል ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ አድርጎታል ማለት ይቻላል። ስለዚህም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ያለው መንግስት ህዝባዊ ሳይሆን የካፒታሊስት መንግስት(The Capitalist State) እየተባለ ነው የሚጠራው። ይህ ጉዳይ በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ሊያከራክረን የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም የእነ ላይብኒዙ ጥበባዊ መንግስት ተምኔታዊ ነው ማለት ይቻላል።

ለማንኛውም የአንድን ህብረተሰብ ዕድል ከራስ ፍላጎት አንፃር በመመልከት የሚደረግ ትግል ወይም ፖለቲካዊ አካሄድ አንድ ህዝብ ነፃ እንዳይወጣ መንገዱን እንደመዝጋት ይቆጠራል። በትንሽ ዕውቀት መኩራትና መዝናናት የመጨረሻ መጨረሻ አንድ አገርና ህዝብ እንዲፈራርሱና አቅጣጫም እንዲያጡ እንደማድረግ ይቆጠራል። መንፈስን ሳያድሱ ወይም ከማንኛውም ዕቡይ ፀባይ ነፃ ሳይሆኑ የሚደረግ ፖለቲካዊ አካሄድ የሳይንስንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ይገታል። አንድ ህዝብ ፈጣሪ እንዳይሆንና የእራሱን ዕድል በእራሱ በመወሰን ጠንካራና የተከበረ ማህበረሰብ እንዳይመሰርት ያደርጋል። በተለይም በዛሬው ወቅት የተለያዩ ኃይሎች ዝም ብለው በሚፈነጩበትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በሚያሳስቱበት ወቅት ሀቀኛውን ከሀሰተኛው፣ አልሚውን ከአጥፊው ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። አንድን ድርጅትም ሆነ ግለሰብ፣ ከየትኛውም ብሄረሰብ ይምጣ መመርመርና፣ የሚናገረው ነገር ትክክልና ትክክል አለመሆኑን መረዳት የሚቻለው በትክክለኛ የዕውቀት መነፅር  መመርመር የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው። ማንኛውም ህብረተሰብን የሚመለከት ነገር ሁሉ በሳይንሱ መመርመርና ማረጋገጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህንን ትቶ በጭፍን እንጓዝ ማለት አገርን እንደማጥፋት ይቆጠራል።

ተጨባጭ ሁኔታዎችን በትክክል የማንበብ አስፈላጊነት!

በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የአንድን ህብረተሰብ ዕድገትና ሁኔታ መመርመሪያ ዘዴዎች ፍልስፋናና የማርክሱ የማቴሪያሊስት መንገዶች ናቸው።  የመጀመሪያው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ ፖለቲካዊም ሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር የሰው ልጅ ጭንቅላት በትክክለኛ ዕውቀት ለመታነፅ ባለመቻሉ የሚል ሲሆን፣ የማርክሱ አካሄድ ደግሞ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሰፈነ የምርት ግኑኝነት ሁኔታና(Social Relationship) አብዛኛውንና ስትራቴጂክ የሆኑ ሀብቶችን የሚቆጣጠር  የህብረተሰብ ክፍል በፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ ማሳደርና የአንድን ህዝብ አኗኗር ሁኔታ መደንገግ ይችላል ይላል። በሌላ ወገን ግን በፍልስፍና ዓለም ውስጥ፣ ወይንም አንድን ሁኔታ በማንበብ ረገድ ሁለት ዐይነት አመለካከቶች አሉ። አንደኛው አንድን ነገር ሁለንታዊ በሆነ ዘዴ ማንበብ ሲሆን፣ በተለያዩ ነገሮ መሀከል መተሳሰርና ተፅዕና መደራረግ አለ ይላል። ስለዚህም አንድ ነገር ከታች  በመነሳት ከፍ እያለና እየተወሳሰበ የሚያድግ ሲሆን፣ በተለይም ህይወት ያለውና አርጋኒክ የሆኑ ነገሮች ለማደግ ውስጣዊ ኃይል አላቸው። ስለሆነም በዚህ ፍልስፍና መሰረት ቋሚ ነገር ወይም እዚያው ባለበት ረግቶ የሚቀር ነገር የለም። ሁለተኛው፣ ኢምፔሪካል ሳይንስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ የጥናቱ መነሻም ነገሮችን በተናጠል ወስዶ መመርመርና አንድ ውጤት ላይ መድረስ ነው። ይህ ሳይንስ ፖዝቲቭ ሳይንስ ተብሎ በመጠራት ሲታወቅ ወደ ኋላ በመሄድ የነገሮችን አመጣጥ እንድንመረመር አያስችለንም። „በተጨባጭ“ ነገሮች ላይ ወይም ፋክትስ ተብለው በሚጠሩ ነገሮች ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን በነገሮች መሀከል መተሳሰርና ተፅዕኖ መደራረግ የለም። ስለዚህም ነገሮች ውስጣዊ የሆነ የማደግ ኃይል የላቸውም። ህብረተሰብም እንደዚሁ የሚለወጥና የሚሻሻል ሳይሆን በተወሰኑ ስዎች ቁጥጥር ስር በመውደቅ እዚያው በዚያው የሚሽከረከር ነው። ይህ ዐይነቱ „ሳይንስ“ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘና በተለይም እንደኛ ያሉ አገሮችን የሚያተረማምስና ለጦርነት የሚጋብዘን ነው። በአጠቃላይ በዓለም ላይ ያሉ የታወቁ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በሙሉ ይህንን ሳይንስ መመሪያ በማድረግ ነው ዓለምን የሚያተረማምሱት።

የመጀመሪያውን የፍልስፍና አመለካከት ከተቀበልን አንድ ህዝብ በመንፈስ ተሀድሶ አማካይነት ነው ነፃነቱን መቀዳጀት የሚችለው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮች የፍትህ ጥያቄዎች ናቸው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ራሱ የገዢው መደብ በራሱ ዓለም ውስጥ ስለሚኖር የህዝብን ችግሮች የማየት ኃይሉ የደከመ ነው። ችግሩን መፍታት የሚቻለው በጦርነት ሳይሆን ሁሉ-ገብ የሆነ ንቃተ-ህሊና እንቅስቃሴ ማካሄድ ሲቻል ብቻ ነው ይላል። ወደ ማርክሱ የማቴሪያሊስት ቲዎሪ ስንመጣ ደግሞ በመደብ ትግል አማካይነት ነው በተለይም የሰራተኛውን መደብ ከተተበተበበት የጭቆና ሰንሰለት ነፃ ማውጣት የሚቻለው። ይሁንና ግን ማርክስ የምርት ኃይሎች ከማደጋቸው ወይም ከመዳበራቸውና በተለይም የወዝ አደሩ መደብ ንቃተ-ህሊናው ከፍ ከማለቱ በፊት አብዮት መካሄድ አለበት ብሎ አልሰበከም። ማርክስ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት በማንሳት በዚህና በተስፋፋ የኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት የወዝአደሩ መደብ በመተሳሰር እንደ ኃይል ይወጣል ይላል። በዚህም አማካይነት ንቃት-ህሊናውን በማዳበር ማንነቱን ያውቃል። ባጭሩ በአንድ አገር ውስጥ አብዮት ለማካሄድ የግዴታ የማቴሪያልና የመንፍስ ሁኔታዎች እንዲሁም ድርጅታዊ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ በደንብ ያስቀምጣል። ሌኒንዝም ይህንን የማርክስን አስተሳሰብ ይደግፋል። ለምሳሌ ስዊዘርላንድ ወደ 17 ዓመታት ይህል በኖረበት ጊዜያት የህብረተሰቡን አደረጃጀትና ጠቅላላውን የመንገድና የቤት አሰራሮች ይመለከታል። ህዝቡም ተመቻችቶ የሚኖር መሆኑን ሲመለከት „እዚህ አገር ስለአብዮት ማውራት እንደ ዕብድነት ይቆጠራል“ ብሎ ይናገር ነበር። በተጨማሪም ከሙኒክ ሆኖ የቅስቀሳ ጋዜጣዎችን እያሳተመ ወደ ራሺያ ለመላክ ሙኒክ ይመላለስ ስለነበር ቡና ወይም ቢራ ቤቶች ይገባ ነበር። ይህንን በጥብቅ የተከታተለው ሌኒን „ቢራቤት ውስጥ የመደብ ልዩነት የማይታይበት“ ነው ብሎ ተናግሯል። ይህ የሚያሳየው ምንድነው? ማርክስም ሆነ ሌኒን በጭፍኑ የግዴታ አብዮት መካሄድ አለበት ብለው አልሰበኩም ወይም አላስተማሩም። ይህንን የማነሳው አለመግባባትን ለማስወገድና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ወይም አንድ ህዝብ የሚገኝበትን የማቴሪያልና የስነ-ልቦና፣ እንዲሁም የባህል ሁኔታ በቅጡ ማጥናትና ማንበብ ከብዙ ስህተቶች እንድንቆጠብ ስለሚያደርገን ነው።

ያም ሆነ ይህ በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ምርምር ከህብረተሰብአዊ ድርጊትና፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግኑኝነትና እርስ በእርሱ በኢኮኖሚም ሆነ በሌላ ነገር ከሚያደርጋቸው ግኑኝነቶች ውጭ በመሆን አይደረግም። ታሪክን ታሪክ የሚያሰኘው አንድ ህዝብ እራሱን ለማሽነፍ ሲል በተፈጥሮ ላይ የሚያደርገው ቁጥጥርና፣ በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን (Organic and non-organic) በመለወጥ መጠቀሚያ ሲያደርጋቸው ብቻ ነው። በመቀጠልም፣ ታሪክን ታሪክ የሚያሰኘው አንድ ማህበረሰብ ከተማን ሲገነባ፣ የባህል ወይም የሃይማኖት ማዕከሎችን ሲያቋቅም፣ ንግድና ዕደ-ጥበብን በማስፋፋት እንደ ማህበረሰብ ሲተሳሰርና ወደ ሲቪል ህብረተሰብ ሲለወጥ እንደዚህ ዐይነቱ አገር ታሪክ አለው ይባላል። በሄገልም ሆነ በካንት መሰረት ከዚህ ውጭ የሚታዩ ታሪኮች እንደ ሚቶሎጂ የሚቆጠሩ ናቸው። በእነሱ ዕምነት ታሪክን መስራት የሚቻለው ካለህበት ሁኔታ በመነሳት እንጂ ወደ ኋላ በመጓዝና እንደዚህ ነበርን በማለት አይደለም። ባጭሩ ታሪክ የአንድን ህብረተሰብ ችግር መፍቻና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማፍለቂያ መሳሪያ ሊሆን በፍጹም አይችልም። በሌላ ወገን ግን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገቶች በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የሚገለጹና የሚካሄዱ ወይም የተወሰኑ ቅድመ-ሁኔታዎች ሲሟሉ የሚፈጠሩ ናቸው።  ከዚህ ባሻገር በአውሮፓ የህብረተሰብና የባህል ታሪክ ውስጥ የሰው ልጅ ወደ ፊት መመልከትና በግልጽ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚጣደፍና አትኩሮውም ችግርን በማስወገድ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ አንድ ማህበረሰብ ታሪክን ለመስራት እንደሚችል ያረጋግጣሉ። አዲስ ታሪክ መስራት የሚቻለው ለመንፈስ ተሃድሶ የሚያመቹ የቀድሞ ባህሎችን ወይም ዕውቀቶችን በማስፋፋትና ከአዲሱ ሁኔታ ጋር እንዲዛመዱ በማድረግ እንጂ፣ እንደ ኢሬቻንና አባገዳ የመሳሰሉትን ለፈጠራና ለዕድገት የማያመቹ፣ የሰው ልጅ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝበት ወቅት ያደርጋቸው የነበሩ ነገሮችን እንደባህል በመቁጠርና፣ ህዝብን በተለይም ወጣቱን በማደንቆር አይደለም ዕውነተኛ ነፃነትና ዕድገት የሚገኘው። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ የታሪክ ወቅት ካለማወቅ የተነሳ የተደረጉ ድርጊቶችን በማንሳትና በማውራት ወይም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የማያመቹ ነገሮችን እንደባህል አድርጎ በመቁጠርና በማክበር አይደለም ስልጣኔ ሊመጣ የሚችለው።  በዚህም መልክ አንድ ማህበረሰብ መፍጠርና ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ በፍጹም አይችልም። አንድ ባህል የማሰብ ኃይልን ከፍ የማድረግ ብቃትነት እስከሌለው ድረስ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገትን ይገታል። በሌላ ወገን ደግሞ የሰው ልጅ ማቴሪያላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እንደመሆኑም መጠን እራሱን ከአንድ ዐይነት ዕምነት ጋር ቢያገናኝ ክፋት አይኖረውም። እንዲያውም የማቴርያል ዕድገትና አንዳች ዐይነት ዕምነት ሲጣመሩ ማንኛውም ሰው ሞራሉ ይጠነክራል። ይሁንና ግን እንደዚህ ዐይነት ዕምነት የየግለሰቦች ምርጫ መሆን ያለበት እንጂ ከላይ በአንድ አካል የሚጫን መሆን የለበትም። ለማንኛውም የአውሮፓው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ችግሮችን በመፍታት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ወደ ፊት መመልከትን እንጂ ወደ ኋላ በመመለስ እንደዚህ እንባል ነበር፣ እንጨቆን ነበር፣ እንቋሸሽ ነበር፣ ባህላችንን ወይም ዕምነታችንን እንዳናከብር ግፊት ይደረግብን ነበር…ወዘተ. እየተባለ ከህብረተሰብ ዕድገትና ከንቃተ-ህሊና ውጭ ነገሮች እየታዩ ጊዜ ማሳለፍ የተለመደ ነገር አይደለም።

ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ  የምናየውና የምንሰማው ነገር በሙሉ ስልት የሌለውና በአንድ ወቅት የነበረን የማህበረሰብ ንቃተ-ህሊናና የማቴሪያል የዕድገት ደረጃ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን የራስንም ታሪክ በደንብ ያልመረመረ ነው። በስሜት ላይና በወሬ ወሬ ላይ የተመሰረተ እንጂ አንዳችም ዐይነት ፍልስፍናዊም ሆነ ሳይንሳዊ፣ እንዲሁም የቲዎሪ መሰረት የሌለው ነው። በኢምፔሪካል ደረጃም የተረጋገጠ አይድለም።  በሌላ አነጋገር፣ አንድ ድርጅትም ሆነ ምሁር ነኝ ባይ ወይም የፖለቲካ አክቲቪስት ነኝ ባይ የአንድን ህብረተሰብ ታሪክ በአንዳች የፍልስፍና መነፅርና ሳይንስ ሳያነብና በሳይንስ የሚረጋገጥ ሀተታ እስካልሰጠ ድረስ እንደዚህ ዐይነቱ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ተልዕኮው ጥፋትና በተጨባጭ ሲታይ ዕድገት እንዳይመጣ የሚታገል ነው። አንድ ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ችግሮችን እንዳይቀርፍ እንቅፋት ለመፍጠር የሚሯሯርጥ ነው። የአንድ ህዝብም ሆነ፣ የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሄረሰብ አባል የሆነ ለመኖር የግዴታ መብላትና መጠጣት እንዲሁም መጠለያ ማግኘት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ  ለመስራት የሚችልና ለአቅመ-አዳም የደረሰ ሰው መስራት አለበት። ራሱን በመቻል የህብረተሰብ አካል መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ነው በአንደ በአካባቢም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ ብሄራዊ ሀብት ሊፈጠር የሚችለው። ከዚህ ውጭ ብሄረሰብን ወይም ጭቆናን አስታኮ የሚደረግ ቅስቀሳ በተጨባጭ ሲታይ አንድ ማህበረሰብ የዝንተ-ዓለሙን በድህነት ዓለም ውስጥ ዘፍቆ እንዲኖር የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ በሆነው የአገር ግንባታ ክንዋኔ ውስጥ ከመሳተፍና ራስን ከመቻል ይልቅ አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ነን የሚሉ ምንም ሳይሰሩ ወዲህና ወዲያ በመንቀሳቀስ ወይም በቪላ ቬት ውስጥ በመቀመጥ በፌስ ቡክ አማካይነት፣ ወይም ደግሞ መንግስት በፈቀደላቸው  የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በመውጣት በማስረጃ ያልተረጋገጠ ወሬ በማራገብና የጥላቻ ወሬ በማውራት ህዝባችን ሰላም እንዳይኖረው ለማድረግ በቅተዋል። በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ ከሌላ አካባቢ የመጣ ሰውና ለብዙ ዐመታት እዚያው የሚኖር በነፃ እንዳይንቀሳቀስ እየተደረገ ነው። በዚህም አማካይነት በብዙ የኦሮሚያ ከተማዎች የንግድ እንቅስቃሴና የምርት ክንውን እየተዳከሙ በመምጣት ላይ ናቸው። ለመሆኑ መንግስትና የክልሉ አስተዳዳሪ ይህንን ሁኔታ ነው ወይ የሚፈልጉት? በግልጽ ቢነግሩን ለመዘጋጀትና የቁርጣችንን ለማወቅ ይረዳናል።

እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ህብረተሰብና እንደ ባህላዊ(Social and Cultural History) ታሪክ በደንብ አልተተረጎመም፤ አልተጻፈምም። የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ በንጉሶች ላይ የተመሰረተ እንጂ የህዝቡን የቀን ተቀን ኑሮ፣ ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ግኑኝነትና፣ እንዲሁም እርስ በእርሱ በሚያገናኘው እንደ ንግድና እንደ ስራ-ክፍፍል ዐይነት ላይ ያተኮረ የታሪክ አጻጻፍ አይደለም የተለመደው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡ እራሱ በግብታዊነት ወይም ተገልጾለት የፈጠራቸው እንደ እርሻ ባህል፣ ምግብ አሰራር ዐይነት፣ እንደ ጠላና ጠጅ፣ እንዲሁም ካቲካላ አጠማመቅ፣ የልብስ አሰራርና የተለያዩ የዕደ-ጥበብ ስራዎች እንደ ታሪክ ቅርጽና ባህላዊ ክንውን ተደርገው ባለመወሰዳቸው ሁላችንም ስንረባረብ የነበረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የጨቋኝ ስርዓት እንደነበረና፣ ስርዓቱም በጨቋኝና በተጨቋኝ ብቻ እንደሚገለጽ ተደርጎ የሚወሰድ እንጂ በፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያም እዚያው በዚያው ባህላዊ ክንውኖችና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ዕድገት እንደነበር በፍጹም ለጥናትም ሆነ ለክርክር አይቀርብም። በተለይም በሙዚቃ ላይ የተደረገው ለውጥ፣ የፊደል አቀራረጽ ዕድገት፣ ግዕዝና አማርኛ እንደመነጋገሪያና ሃሳብን መግለጫ ቋንቋ በመሆን ለስነ-ጽሁፍ ዕድገት የነበራቸውንና ያላቸውን ከፍተኛ ሚናና አስተዋፅዖ በደንብ የተነተነ የለም። በዚህ ረገድ ዛሬ ዘመቻ የሚካሄድበት የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና ቤተክርስቲያን ለህብረተሰቡ መተሳሰርና ለዕድገትም የነበራቸውን አስተዋፅዖ ተብራርቶ አይቀመጥም። በፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያ ዕውቀት የሚባለው ነገር የሚፈልቀው ከቤተክርስቲያን በኩል ነው። አብዛኛዎች ነገሮች የፈለቁት በዚህ ዐይነቱ ተቋም አማካይነት ነው። ከዚህ ስንነሳ የባህልን ዕድገትና አንዳንድ ተቋማት ለዕድገት ያላቸውን አስተዋፅዖ ሳይመረምሩ ቤተክርስቲያንን ማቃጠልና የሃማኖት አባቶችን መግደል ትልቅ የታሪክ ወንጀልና በይቅርታ የማይታለፍ ጉዳይ ነው። የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለማዳከምና እንዲያም ሲል ለማጥፋት በውጭ ኃይሎች በሚደገፉ የእስላም አክራሪዎችና አግሬሲብ በሆነና በረቀቀ መልክ የዘመኑ የክርስትና ሃማኖት አራማጆች የሚያደርጉት ዘመቻ አለመረጋጋትን መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን የእርስ በእርስ ጦርነትም እንዲመጣ የሚጋብዝ ነው። እነዚህ ኃይሎች እንደዚህ ዐይነቱን ጭንቅላትን የሚያደነዝዝ ሰበካና ቅስቀሳ ከማድረግ ይልቅ በፈጠራ ስራ ላይ ቢያተኩሩና የህበረተሰብአችንም የተወሳሰቡ ችግሮች የሚቀረፉበትን ዘዴዎች ቢያሳዩን የታሪክ ተልዕኮአቸውን ተወጡ ማለት ነው።

ለማንኛውም ካርል ማርክስ አንድ ቦታ ላይ እንዳለው በአውሮፓው ማህበረሰብ ውስጥ ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረቱ የተጣለው በፊዩዳሉ ስርዓት ውስጥ ነው። ቤተ-ክርስቲያናት የተቋቋሙት፣ የገበያ አዳራሾች የተገነቡት፣ የዕደ-ጥበብና ንግድ የተስፋፉት፣ እንዲሁም የመጀመሪያው የሳይንስና የፍልስፍና ምርምሮች የተፈጠሩትና የተስፋፉትም በፊዩዳሉ ስርዓት ውስጥ ነው። እነዚህ እያበቡና እየተስፋፉ ሲሄዱ ከአረጀው ስርዓት ጋር አብረው ለመኖር ያልቻሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። ሄገልስም ሆነ ማርክስ ዲያሌክቲክ በሚለው ሀተታቸው የአንድን አዲስ ሁኔታ መፈጠርና ወደሌላና ወደ ተወሳሰበ ነገር መቀየር የህብረተሰብ ዕድገት ህግ መሆኑን ያስተምራሉ። አንድ ዘር ከተዘራ በኋላ ወደ ስር፣ ወደ ግንድና ቅጠላ ቅጥል፣ እንዲሁም ፍሬውን የሚይዙት ቅርንጫፎች እንደሚለወጥ ሁሉ አንድም ህብረተሰብ በዚህ ዐይነቱ ዲያሌክቲካዊ ሂደት( Thesis, Anti-thesis and syntehsis) ከዝቅተኛ ደረጃ ወደ ተሻሻለና ወደ ተወሳሰበ የመለወጡ ጉዳይ ተፈጥሮአዊ  ህግ ነው።  ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ ህብረተሰቡን ሊያሰታስስሩ የሚችሉ ነገሮችና አገሩን አገሬ ብሎ እንዲጠራ ያሰኙት ነገሮች በሙሉ በአብዛኛው መልኩ በፊዩዳሉ ስርዓት ውስጥ የፈለቁና የዳበሩ ናቸው። በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ ለምን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊታይ አልቻለም? ለምንስ ሳይንስና ሊዳብር አልቻለም? ለምንስ የስራ-ክፍፍል በመዳበርና ንግድ በመስፋፋት ከተማዎችና መንደሮች ሊገነቡ አልቻሉም? ለሚሉት ጥያቄዎች ለጊዜው በቂ መልስ መስጠት አይቻልም። ይሁንና ግን በዚህ ላይ ጥናት ማጥናቱና መመራመሩ አንድን አገር እንደ ማህበረሰብ ለመገንባት እንደ አስፈላጊ ነገር ሆኖ መታየት ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል።

ለማንኛውም የፊዩዳሉ ስርዓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተስፋፋ እንደነበረና፣ በተለይም ገበሬው ወደ ስምንት መቶ ዐመታት ያህል በዚህ ስርዓት ውስጥ በመበዝበዝ አሪስቶክራሲውንና የፊዩዳሉን መደብ፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ሲመግብ የነበረ የህብረተሰብ ኃይል እንደነበር ይታወቃል። ይህም ማለት ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ስንመጣ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የፊዩዳሉ ስርዓት በፍጹም አይታወቅም ወይም ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ያለ ስርዓት ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በሌላ አነጋገር በደቡብ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ህዝብ ይበዘብዙ የነበሩ በዚያን ጊዜ በየአካባቢው የነበሩ የገዢ መደቦች እንጂ በሰሜኑ ክፍል የሚገኘው ፊዩዳላዊ አገዛዝ አልነበረም። ይህ ጉዳይ በተለይም አምስቱ ነገስታት በሚባሉት እንደ ከፋና ሃዲያ በመሳሰሉት ግዛት ውስጥ የነበረና ገና እንደ ፊዩዳሉ ስርዓት በደንብ ጎልቶ ባልወጣበት አካባቢ የሚታወቅ ነበር። ይሁንና ግን በደቡብ የሚገኙት ነገስታት ለክርስቲያኑ ነገስታት ግብር ይከፍሉ እንደነበር ይታወቃል።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? እራሱ አማራ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል በእራሱ በአማራ የገዢ መደብ የሚበዘበዝ እንጂ ጠቅላላው አማራ በደቡቡ ህዝብ ላይ በመዝመት የሚበዘብዘው አልነበረም። በሌላ ወገን ግን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የፊዩዳሉ ስርዓት ወደ ደቡቡ ክፍል ሲስፋፋ አዲስ ዐይነት የህብረተሰብ ግኑኝነት(Social and Political Relationship) እንደተፈጠረ የማይታበል ሀቅ ነው። ይህ ዐይነቱ መስፋፋት በራሱ እንደ አዲስ ዐይነት የማህበረሰብ ለውጥም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። እስከዚያን ጊዜ ድረስ በአደንና በከብት አርቢነት የሚተዳደሩ ጎሳዎችን ተቀማጭ እንዲሆኑ በማድረግ የእርሻ ባህል ሊስፋፋ ችሏል። በዚያው በነበርንበት እንቅር ካልተባለ በስተቀር የፊዩዳሉ ስርዓትና የክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት በዚያ ለሚገኘው ማህበረሰብ አዲስ ዕምርታ ሊሰጠው ችሏል ማለት ይቻላል። ይሁንና ይህ ዐይነቱ መስፋፋት በከፍተኛ ዕውቀት ያልተደገፈ ስለነበር ዕድገቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር አልቻለም። ይህ ዐይነቱ ድክመት የጠቅላላው የአገሪቱ ድክመት ጉዳይ ስለሆነ ሁኔታውን ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ማገናኘት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህን ሳያደርጉ በጨቋኝና በተጨቋኝ ብሄረሰቦች መሀከል የነበረና፣ ስርዓቱም በነፍጠኞች ይመራ ነበር እያሉ በጭፍኑ የተሳሳተና በማስረጃ ያልተደገፈ አስተሳሰብን ማስፋፋትና ቅስቀሳ ማድረግ በቀላሉ ልንወጣ የማንችለው ማጥ ውስጥ ነው የሚከተን፤ ከቶናልም ማለት ይቻላል።

ይህንን ጉዳይ ከአውሮፓው፣ በተለይም ከጀርመኑ የባህል ለውጥና ዕድገት ጋር ብናወዳድረው በፕረሺያ አካባቢ ስልጣንን ያየዙት ነገስታትና የገዢ መደቦች አካባቢያቸውን ለማሰልጠን ሲሉ የተማሩ ሰዎችን ወይም ደግሞ በሃይማኖት ሰበብ የተባረሩ፣ በተለይም ሁጎኖቶች በመባል የሚታወቁትን ከሆላንድና ከፈረንሳይ በመጋበዝ ወይም መጠጊያ በመስጠት ህዝባቸውን እንዲያሰለጥኑና ግዛታቸውም እንዲያድጉ ያደርጉ ነበር። በዚህ መልክ ነው በብዙ አውሮፓ አገሮች ውስጥ ዕድገት የሚባለው ነገር ሊታይ የቻለውና የካፒታሊዝም ዕድገት ሊፋጠን የቻለው።  ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣም ግን በነፍጠኛ ስም የሚሰደቡትና ይገደሉ የነበሩት የቤተ-ክህነት ትምህርት የነበራቸውና መጻፍና ማንበብም የሚችሉ ነበሩ። በጊዜው ከእነዚህ የተሻለ የተማረ ሰው ስላልነበር  እነዚህን የመሳሰሉትን የቤተ-ክህነት ትምህርት የነበራቸውን ለአስተዳደር ስራ በአዳዲሶቹ ግዛት ማሰማራት ታሪካዊ ግዴታ ነበር። ይሁንና ግን ይህንን ጠምዝዞ  አቅኚዎችን እንደወራሪዎች አድርጎ መቁጠርና እያሳደዱ መግደል የህብረተሰብን ዕድገት ካለማወቅ የሚመነጭ አደገኛ አስተሳሰብ ነው።

ወደ ሌላ ጉዳይ ስንመጣ አንድ ማዕከላዊ መንግስት ሲቋቋምና ካፒታሊዝም ወደ አገራችን ሲገባ ይህ ሁኔታ አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግኑኝነት እንደፈጠረ የማይታበል ጉዳይ ነው። በአፄ ምኒልክ ዘመንም ሆነ የኋላ ኋላ አማራውን ብቻ የሚወክልና የሚጠቅም የገዢ መደብ አዲስ አበባ ውስጥ በፍጹም አልተቀመጠም። በተለይም ይህ ጉዳይ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ግልጽ ሆኖ የወጣና፣ ዕድገት አለ የሚባል ከሆነ በዕድገት ስም የሚደረገው እንቅስቃሴ በአብዛኛው መልኩ ወደ ደቡቡ ኢትዮጵያ ክፍል ያደላ ነበር። በዚህ መልክ ከሩቅ ሆነው የሚያሳርሱ ባላባቶች(Absentee Landlords) በመፈጠር የብዝበዛው መጠንና ግኑኝነቱ  ለየት ባለ መልክ የሚካሄድ ነበር። ስለሆነም በካፒታሊዝም መስፋፋት አዲስ የፖለቲካና የህብረተሰብ ግኑኝነት ሊፈጠር ቻለ እንጂ ብሄረሰብን ተገን ያደረገና፣ አንድን ብሄረሰብ ብቻ በመጥቀምና ሌላውን በመጉዳት ወይም በመበዝበዝ የሚገለጽ ስርዓት በኢትዮጵያ ምድር አልሰፈነም። የካፒታሊዝም መስፋፋት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ግኑኝነት በአዲስ መልክ እንዲዋቀር በማድረግ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በተለያየ ሙያ ለመሰልጠን የቻሉ ብቅ ብቅ ማለት እንደቻሉ የኢትዮጵያን የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ለመረመረ በደንብ ሊረዳው ይችላል። ይህንን ሁኔታ በተሻለ መልክ የሚለውጥና ሪፑብሊካናዊ አገዛዝ ሊቋቋም አለመቻሉ በጊዜው የነበረውን የአስተሳሰብና የህብረተሰብ ዕድገት ሁኔታ የሚያሳይ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማዕከላዊ መንግስቱ ከዚህ ዐይነቱ መጠነኛ የሆነ የጥገና ለውጥ አልፎ ለመሄድና ሁለ-ገብና መሰረታዊ የሆነ ዕድገት የማምጣት ኃይልም ሆነ ንቃተ-ህሊና አልነበረውም። ከዚህም በላይ ደግሞ የሪፑብሊክን አርማ ይዞ የሚታገል የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይልና ህዝባዊ እንቅስቃሴ ባለመኖራቸው የፊዩዳሉና የተዘበራረቀው የካፒታሊስት የአመራረት ስልት እዚያው በዚያው የህብረተሰባችንን ዕድገትና የመኖር ሁኔታ የሚደነግጉ ለመሆን በቁ። የአውሮፓን የባህልና የህብረተሰብ ታሪክ የተመለከትን እንደሆነ ለውጥ የሚባለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ መልክ የሚገለጽ ሊመጣ የቻለው ከስልጣን ውጭ በነበሩ ምሁሮች አማካይነት ነው። በጊዜው እያደገ በመጣው ዕውቀትና አዲስና የተገለጸለት ህብረተሰብአዊ ኃይል በመገፋት ነው መንግስታት ወደ ውስጥ ያተኮረና ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚና የባህል ፖሊሲ መከተል የቻሉት። ምሁራዊ ኃይል በሌለበት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራ በማይታወቅበት፣ በፍልስፍና ላይ ርብርቦሽ በማይደረግበት አገር ውስጥ ውስጣዊ-ኃይል ያለውና ዕድገትን ወይም ለውጥን የሚፈልግ የህብረተሰብ-ኃይል ለማፍለቅ በፍጹም አይቻልም።

ለማንኛውም የተማሪው እንቅስቃሴና፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ ነፃ አውጭ ነን የሚሉ አፈንጋጭና ጽንፈኛ ኃይሎች በሚተረጉሙት መልክ ሳይሆን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ታሪክ መተርጎም ያለበት በሌላ መልክ ነው። ይህ ዐይነቱ የተሳሳተና በምድር ላይ የሚታየውን ሁኔታ በደንብ ያላገናዘበ አተረጓጎም በተለይም በአማራው ማህበረሰብ ላይ ጥርጣሬ በማሳደርና ነፍጠኛ የሚል ስድብ በማንጋጋት በህብረተሰቡ ዘንድ መቃቃር እንዲፈጠር ተደርጓል። ጠቅላላው ህዝብ እርስ በእርሱ እየተጠራጠረ እንዲኖር የማይሆን ቃላቶች በማስፋፋት ከቁም ነገር እንድንዘናጋ ተደርገናል። በአንድ አገር ውስጥ የሚነዙ ፅንሰ-ሃሳቦች በደንብ ካልተጠኑና ከሁኔታው ጋር እስካለተገናዘቡ ድረስ እንደ እነዚህ ዐይነት ፅንሰ-ሃሳቦች እንደ ተፈጥሮአዊ ባህርይ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። በሌላ አነጋገር፣ አማራ ነፍጠኛና ጉረኛ፣ እንዲሁም ሌላውን የሚንቅና፣ ይህም ተፈጥሮአዊ ባህርይው  እንደሆነ ተደርጎ ይወራል። ሌላው ይህንን ሲሰማ ትክክል ነው ብሎ በማመን ማስተጋባት ይጀምራል። በውሽት የተካኑት ሻቢያና ወያኔ አሁን ደግሞ ኦነግና ሌሎች የኦሮሞ ጽንፈኞች እንደዚህ እያሉ በማውራት ነው ህብረተሰቡ በአንድነት በመነሳት አገሩን እንዳይገነባ የሚጥሩት። ስራቸው በሙሉ እጅግ ወደ ኋላ የቀረና አረመኒያዊ ተግባር ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ በፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያ የሚታወቅ ጉዳይ አልነበረም። ካለ ደግሞ ከንቃተ-ህሊናና ከዕውቀት ማነስ የሚመነጭ እንጂ ሆን ብሎ የሚደረግ ወይም የሚወራና ሌሎችን ዝቅ አድርጎ ለመመልከት ተብሎ አልነበረም።

ለማንኛውም በፊዩዳሉ መደብና በተቀረው ማህበረሰብ የነበረው ግኑኝነትና ስርዓቱ በአጠቃላይ ሲታይ እንደጨለማ ስርዓትና ምንም ዐይነት የሞራል ሚዛን ወይም መመሪያ እንደሌለው ተደርጎ መቅረብ ያለበት ነገር አይደለም።  አንዳንዶች ሌላውን የጠቀሙ ይመስል ሁኔታውን በደንብ ሳያጠኑ ዝምብለው የፊዩዳሉ ስርዓት ጨለማና በዝባዥ ብቻ ነበር ብለው የሚያወሩ  በጊዜው  የነበረውን  የንቃተ-ህሊና ሁኔታና የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል አለመኖርን ያላገናዘበ አባባል ይመስለኛል። በአጠቃላይ ሲታይ በአንዳንድ ከተሞች የፊዩዳሉ መደብ አንዳንድ በዓሎችን ምክንያት በማድረግ በሬ ለክርስቲያኑም ሆነ ለእስላሙ በማረድና በመጋበዝ የህብረተሰቡ አካል እንደሆነ ያሳይ እንደነበር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በተለይም ሰርግና ሌሎች ባህላዊ በዓሎች በሚከበሩበት ጊዜ የፊዩዳሉ መደብ በአካባቢው የሚገኙ ኗሪዎችን በመጋበዝ በደህና ጊዜ የበዘበዘውን በዚህ መልክ ያካፍል ነበር። ባጭሩ ሀቁ ይህ ነው። እንደዚህ ስል እንዲያው ስርዓቱ በጣም ጥሩ ነበር ብዬ ለመጻፍ ሳይሆን አንድ ነገር ሲወራም ሆነ ሲጻፍ በጊዜው ከነበረው ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትና የንቃተ-ህሊና ሁኔታ በመነሳት ቢጻፍና ቢወራ ማንኛውም ሰው ሁኔታውን በቅጡ ሊገነዘበው ይችላል። ከህብረተሰብ ዕድገትና ከንቃተ-ህሊና ውጭ የሚካሄድ ዘመቻ ለደም መፋሰስ ምክንያት ይሆናል። ጥላቻ እንዲስፋፋ በማደረግ ለዕድገት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች እንዲፈጠሩ ይደረጋል። ይህንን ነው የወያኔ ሰዎችና አሁን ደግሞ የኦነግ ሰዎች ሆን ብለው የሚያወሩት። በዚህ ዐይነት ድርጊታቸው ምን ነገር ለማትረፍ እንደሚችሉ ግልጽ የሆነላቸው አይመስልም። እነውክለዋለን የሚሉትን ብሄረሰቦቻቸውን የጠቀሙ ከመሰላቸው በጣም ተሳስተዋል። እንዲያውም በራሱ እንዳይተማመንና  እንደ ነፃ ዜጋ እንዳይንቀሳቀስ ነው የሚያደርጉት። እራሱን አግልሎና በጥርጣሬ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ  እራሱን የህብረተሰቡ አካል አድርጎ ስለማይቆጠር እየፈራና እየተባ ይኖራል። የማሰብ ኃይሉም ስለሚቀጭጭ እንደ ነፃ ሰው እንዳኖር ይፈረድበታል ማለት ነው። በተጨባጭ ሲታይ ወያኔና የኦነግ ሰዎች ይህን የመሰለውን ህዝባቸውን የሚያደነቁር ወንጀል ነው የሚሰሩት። በእነሱ ቁጥጥር ስር ያሉ ሚዲያዎችም በማስረጃ  ያልተደገፈ ሃሳብ በማስፋፋት ህዝባቸውን በማደንቆር ላይ ይገኛሉ።  ሚዲያዎች የማስተማሪያና ዐይንን የመግለጫ መሳሪያዎች ከመሆናቸው ይልቅ እራሳቸውን በደንብ መግለጽ የማይችሉና ህብረተሰብአዊ ግንዛቤ የሌላቸውን ግለሰቦች እየጋበዙ የሚሆነውን የማይሆነውን ነገር በማውራት ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል እየሰሩ ይገኛሉ። በመሰረቱ አንድ ሚዲያ የፕሮግራም ዳይሬክቴርና ፕሮፌሺናል የሆኑና ከመንግስት ወይም ከፓርቲና ከድርጅት ተፅዕኖ ውጭ የሆኑ  ሰራተኞች እንዲኖሩት ያስፈልጋል። ቃለ-መጠይቅ ከመደረጉም ሆነ አንድ ፕሮግራም ከመሰራጨቱ በፊት የብዙ ወራት ዝግጅትና ጥናት ያስፈልጋል። ከዚህ ዐይነቱ የአስረራ ስልት በመውጣትና ከየመንገዱ አክቲቪስት ነኝ የሚለውን ሁሉ እየጋበዙ ገለጻ እንዲሰጥ ወይም የቃለ-መጠይቅ ምልልስ እንዲያደርግ መጋበዝ ኃላፊነት የጎደለው አሰራር ነው። ይህ ዐይነቱ የአሰራር ግድፈትና ፕሮፊሽናሊዝም የጎደለው ስልት በኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ብቻ የሚታይ ስህትት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በአገር ቤት ውስጥ ባሉና ውጭ አገርም በሚገኙ የኢትዮጵያውያን ሚዲያዎች ላይ የሚታይና የተስፋፋ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የብዙዎቹ ሚዲያዎች አሰራር ተራማጅና የተገለጸለት አስተሳሰብ የማይንጸባረቅበት የሆነ መድረክ ነው ማለት ይቻላል።

በአጠቃላይ ሲታይ ከጭቆና ወጣለሁ ብሎና „የነፃነትን አርማ“ ይዞ የተነሳው የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሄረሰብ ኤሊት እራሱን ወደ ጭራቅነት በመቀየር ከፊዩዳሉ ስርዓት የባሰ ሁኔታ እንዲስፍን ነው ያደረገው። ሃይማኖትም ሆነ ምንም ፍልስፍና የሌለው የብሄረሰብ እንቅስቃሴ ስንትና ስንት ሺህ ዘመናት የተገነቡና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ እሴቶችንና ባህሎችን በመበጣጠስ ህዝቡ በፍርሃት እንዲዋጥ ለማድረግ በቃ። ቀሳውስትና አማራ የሆነውን የማህበረሰብ ክፍል ወደ ገደል ውስጥ እየወረወረ በመግደል የነፃነትና የስልጣኔ አራማጅ ሳይሆን የጨለማን ስርዓት የሚናፍቅ መሆኑን አረጋገጠ። በዲሞክራሲ ፈንታ  ፈሺሽታዊ ስርዓትን በማንገስ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ አገደ። በተለይም ወያኔ በዘረጋው በክልል ላይ የተመሰረተ ፌዴሬሽን የሚሉት ፈሊጥ፣ በመሰረቱ ምንም ዐይነት ፌዴራላዊ ባህርይ የሌለው ነፃ ወጡ የተባሉ ብሄረሰቦችን ወደ ኋላ እንዲጓዙ አደረጋቸው። ለብዝበዛ እንዲያመቸው የየክልል መሪዎችን በጥቅም በመግዛት በአጠቃላይ ሲታይ በአገሪቱ ውስጥ የዘረፋ መንግስት(Predatory State) አቋቋመ። በተከተለውና ተግባራዊ በሆነው  የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አገሪቱ ወደ አበባና ወደ ሽንኮራአገዳ ተከላነት፣ እንዲሁም ቡናና ሰሊጥ በማምረት ሌሎች አገሮችን የሚመግብ ስርዓት ፈጠረ። ከሶስይሎጂ አንፃር ደግሞ ምንም ዐይነት የሞራል ገደብ የሌለው የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ የሚመረተው ሀብት ወይም ሪሶርስ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ሚጠቀመው የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈሰ ለማድረግ በቃ። ይህ ዐይነቱ ሁሉን ሀብት፣ ከመብራት እስከ ውሃ ድረስ ተጋሪና በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሆነ የህብረተሰ ክፍል በአገራችን ምድር፣ በተለይም በአዲስ አበባ ለሚታየው የተንሰራፋ ድህነትና የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች እንደ አሸን መፍለቅ የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማድረግ የበቃ  ኃይል ነው። በአንድ በታወቀ የህንድ ሶስዮሎጂስት እንደዚህ ዐይነቱ ሁሉንም ነገር የሚጋራና በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀም የህብረተሰብ ክፍል ሁሉንም አግበስባሽ(Omnivorous) በመባል ይታወቃል።

ከዚህ ስንነሳ አብዮቱ ከከሸፈና የወያኔ አገዛዝ በውጭ ኃይሎች በመታገዝ ስልጣንን ከተቀናጀ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፊዩዳሉ ስርዓት በባሰ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል። ሃይማኖትን ይፈራ የነበረው ህዝብ እሴቱ ስለተበጣጠሰበት በአፍ ካልሆነ በስተቀር እንዳያምን ተገዷል። ባጭሩ ያረጀና በዝባዥ ስርዓት በመባል የሚታወቀው ፊዩዳላዊ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ዘመናዊነትና ወደ ስልጣኔ አላመራም። አስከፊና አረመኔ ወደ ሆነ ስርዓት ውስጥ እንዲወድቅ ነው የተደረገው። በዚህ መልክ የስንቱ ቤት ፈረሰ። ስንትና ስንት ሰው ተገደለ። ስንቱስ እንዲያብድ ተገደደ። ነገሩን በሰከነ መልክ ለመረመረ በዓለም ታሪክ ውስጥ አንድ ማህበረሰብ በዚህ ዐይነት መልክ የተበወዘበትና ምስቅልቅሉ የወጣበት አገር በፍጹም የለም። ከውጭ በመጣ ኃይል እንኳን የአንድ አገር እሴት በዚህ መልክ አይፈራርስም። በዘመነ ፋሺዝም ዘመን በአውሮፓ ምድርም ውስጥ እንደዚህ ዐይነቱ አገርን መበወዝና ደብዛው እንዲጠፋ የተደረገበት አገር የለም። ይህ ነው የእነ መለስና የሻቢያ መሪዎች፣ ዛሬ ደግሞ የኦነግ ጽንፈኞች የስራ ውጤት።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔ፣ የሻቢያና የኦነግ መሪዎች ስልጣኔን የሚጠሉ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውም ሰው መሆናቸውን የተገነዘቡ አይደሉም። በጭንቅላታቸውና በልባቸው ውስጥ ምንም ፀፀጥና ርህራሄ የማይሰማችው፣ የሰው ልጅና ተፈጥሮ ምን እንደሆኑ ያልተረዱና የማይረዱ ናቸው። መንፈሳቸው ለጥበብ፣ ለሙዚቃና ለስነ-ጽሁፍ የተዘጋጀ አይደለም። ስሜታቸው የደነዘዘ ከመሆኑ የተነሳ ሌላውን በማሰቃየትና በመግደል ብቻ ነው የሚደሰቱት። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችን ለመለወጥና በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ ለማሳተፍና ሚናም እንዲኖራቸው ማድረግ በፍጹም አይቻልም። ከእነሱ ጋር መጨቃጨቅ ወይም እነሱን መለማመጥ ጊዜን ማባከን ብቻ ነው።

ተጨባጭ ሁኔታዎችን በትክክል ማንበብ አለብን ስንል የወያኔ አገዛዝ ዘመንንም በትክክል መረዳት ያለብን ይመስለኛል። ህውሃት የአብዮታዊ ዲሞክራሲን  ስርዓት ነው ሲያራምድ የነበረው፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲውም ሶሻሊስታዊ የዕቅድ ወይም የዕዝ ኢኮኖሚ ነው እያሉ በአገራችን ምድር ያልነበረን ስርዓት ማንበብና በዚህ ዙሪያ ትግል እንዲደረግ ማድረግ እጅግ የተሳሳተ አመለካከት ነው። የወያኔ አገዛዝ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ወደ ዘራፊ መንግስትነት የተለወጠ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ፣ በዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያዎችና በዓለም ኮሙኒቲው በመመከርና በመታገዝ የመንግስትን ሀብቶችን ወደ ግል ማዘዋወር(Privatization) በሚል ሽፋን ስም የወያኔ ሰዎች እጅ ውስጥ የወደቀና፣ ብዙ ሀብት ወደ ትግሬ እንዲፈስ የተደረገ ነው። ይህ ዐይነቱ ዘረፋ ወደ ፋሺዝምነት ወደ ተለወጠ የመንግስት መኪና በመታገዝና በውጭ ኃይሎች በመመከር በአገራችን ምድር ላይ ልዩ ዐይነት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግኑኝነት እንዲፈጠር ያደረገ ነው። ስርዓቱ በዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ስር እንዲወድቅ በመደረግ በተለይም የአገራችን ወጣት ሴቶች አበባ ተካይ እንዲሆኑ የተደረገበትና፣ ገበሬው ከመሬቱ እየተፈናቀለ የአገራችን መሬት ለውጭ አልሚዎች በመሰረቱ አጥፊዎች በመሰጠት ሩዝና ስንዴ እየተመረተ ወደ ውጭ የሚጋዝበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የሰሊጥ ተከላ መስፋፋትና በወያኔ ስዎች ቁጥጥር ስር በመሆን ወደ ውጭ እንዲላክ ማድረግ፣ የሽንኮራ አገዳ መትከልና ስኳርን እያመረቱ ወደ ውጭ መላክ…ወዘተ. ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲና ክደቬሎፕሜንታል ስቴት ጋር የሚያይዘው በፍጽም አንዳችም ነገር የለም።

ስለሆነም ዛሬ በአንዳዶች የሚሰጠው ትንተናና በዶ/ር አቢይ ርዕዮተ-ዓለሙን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ብልጽግና ራዕይ ለመለወጥ ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚለው እጅግ የተሳሳተና ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማያንጸባርቅ ነው። ከዚህ ስንነሳ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በባህርይው ፀረ-ዲሞክራሲ ነው የሚለው አባባል ትክክል አይደለም። ፅንሰ-ሃሳቡ በራሱ ፀረ-ዲሞክራሲ ሊሆን በፍጹም አይችልም፤ እራሳቸው ይህንን ዐይነት “ርዕዮተ-ዓለም“-ርዕዮተ-ዓለም ብለን ከጠራነው- የፈጠሩትና እነከተላለን የሚሉት ሰዎች ናቸው ፀረ ዲሞክራሲና ፀረ ነፃነት ኃይሎች። ስለሆነም አንድ ድርጅት ስሙን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ብልጽግና ስለለወጠ ያኔውኑ ዲሞክራት በመሆን የተቀደሰ ስራ ይሰራል ማለት አይደለም። ይህማ ቢሆን ኖሮ ስማቸውን የለወጡ መንግስታትም ሆነ ፓርቲዎች ለህዝቦቻቸው ብልፅግናና ዕውነተኛ ነፃነትን ባመጡ ነበር። የስም መለወጥ ለምን መሰረታዊ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል በምሳሌ ላስረዳ። ለምሳሌ አበበ የሚባል ሰው በጣም ተንኮለኛ ነው። በሰው ላይ ተንኮል ለመስራትና ለመጉዳት ሲል የማያወጣው የማያወርደው ነገር የለም። ተንኮል ከባህርይው ወይም ከደሙ ጋር የተወሃደ ስለሆነ ሁሉንም ባይሆን አንዳንዶችን ለመጉዳት ሲል የማያውጠነጥነው ነገር የለም።  በዚህም ስራው በብዙ ሰዎች የተጠላና የሚያቀርቡትም አይደለም። አንድ ቀን ብልጭ ይልበትና ከዚህ ተንኮሌ በምን ዘዴ ልላቀቅ ብሎ ያወጣል፣ ያወርዳል። ሲያወጣ ሲያወርድ ስሜን በበለጠ ብቀይረው የተንኮል ባህርዬ ይለቀኝ ይሆናል ይልና ስሙን በበለጠ ይቀይራል። ይሁንና ግን ስሙን ወደ በለጠ የቀየረው አበበ ባህርይው አለቅ ብሎት ሌላ ተንኮል ይሰራና ሰውን ይጎዳል። ይህም የሚያሳየው ከአበበ ጭንቅላት ውስጥ የተተከለ መጥፎ ባህርይ ስሙን በመቀየሩ ቀናና ለሰው ልጅ ጥሩ ነገር የሚያስብ ሊሆን አልስቻለውም። አበበ ከዚህ ዐይነት ተንኮለኛ ባህርይው ሊፈወስ የሚችለው ምናልባት የብዙ ዐመታት ቴራፒ ካደረገ በኋላ ይሆናል። ይህም ቢሆን የማይሳካበት ጊዜ አለ። በተለይም ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ በቴራፒ መጥፎ ባህርይን መፈወሰ አይቻልም። ስለሆነም የስም መለወጥ አይደለም አንድን ሰው ዲሞክራት የሚያደርገው።

በሳይንሱ ዓለምም እንደዚሁ አንድ በጭንቅላት ውስጥ የተቀረጸን የአሰራርና የአስተሳሰብ ስልትን ለመለወጥ እንደማይቻል ፖለናዊው የሚክሮ ባይሎጂስትና ፈላስፋው ፕሮፌሰር ሉድዊክ ፍሌክ ያረጋግጣል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ላይ ሆነው የሚሰሩና አንድ የአሰራር ስልትን ያዳበሩ ሌላ የተሻለና የበለጠ ችግር ፈቺ የሆነ የአሰራር ዘዴ በሚፈጠርበት ጊዜ ወይም ደግሞ ያለም ቢሆን ከአስተሳሰባቸው ጋር ከተዋሃደው የአሰራር ስልታቸው በፍጹም ሊላቀቁ አይችሉም ይላል። ይህንን ዐይነቱ አንድ ዐይነት የአሰተሳሰብ ስልት መፈጠርና በጭንቅላት ውስጥ መቀረጽ ፕሮፈሰር ሉድዊክ ፍሌክ „የአስተሳሰብ ስታይልና የአሰታሳሰብ ጋርዮሽነት“ ብሎ ይጠራዋል። ይህንን ዐይነቱን አስተሳሰብ ቶማስ ኩህንም ዘ ስትራክቸር ኦፍ ሳይንቲፊክ ሬቮሉሽን በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ያረጋግጠዋል። ካተ ራዎሮዝም( Kate Raworth)  ዘ ደግነት ኢኮኖሚክስ( Doughnut Economics-Seven Ways to Think Like a 21st-Century Economist) በሚለው ግሩም መጽሃፏ ውስጥ ሃሳባቸውን ትጋራለች። በእነሱ ሳይንሳዊ ምርምርና ውጤት ይህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ጋርዮሽነት በተለይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ቲዎሪንና ፖሊሲን በሚያራምዱ ኢኮኖሚስቶች ዘንድ የተለመደና በፖሊሲው አማካይነት በየአገሮች ውስጥ ህዝባዊ ሀብት ሳይሆን ድህነት ቢፈጠርም ይህ ብቻ ነው ትክክል ነው በማለት በአንድ አገር ውስጥ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንዲያም ሲል ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ሰሞኑን በኢኳዶር፣ ቺሌና አርጀንቲና የምናየው ይህንን ዐይነቱን ከአስተሳሰብ ጉድለት የሚፈጠረውንና ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲና የኢሊቶች ዕብደት የሚያመጣውን ህብረተሰብአዊ ቀውስ ነው። ባጭሩ ኢህአዴግ ስሙን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ብልጽግና ፓርቲ በመለወጡ አባላቱ፣ በተለይም አመራሩ ከመቅጽበት ቅዱስ በመሆን ለሰፊው ህዝብ ብልጽግናን ሊያመጡለት በፍጹም አይችሉም። በተለይም እንደ ወያኔ ዐይነቱ ከአረመኔያውና ከበጥባጭ ባህርዩ በፍጹም ሊላቀቅ አይችልም።

ያም ሆነ ይህ አንድን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ያሉትንም ሰዎች የአስተሳሰብ ስልትና የአስተሳሰብ ጋርዮሽነት ማንበብ ሲቻልና፣ የሚከተሉትንም አጠቃላይ ፖሊሲ በሳይንሱ መንገድ መተንተን ከተቻለ ችግሩ ከምን እንደመነጨ መረዳት ይቻላል። አንድ ሁኔታ በትክክል ሲነበብና ሲመረመር ብቻ ነው ፍቱንና ሳይንሳዊ መልስ ማግኘት የሚቻለው። በመሆኑም አንዳንድ ተንታኝ ነን ባዮች ከዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ ንባብና ግንዛቤ መቆጠብ አለባቸው። የማያውቁትንና በደንብ ማንበብ የማይችሉትን የአንድን ህብረተሰብ ሁኔታ በተሳሳተ መልክና ለአንድ ርዕዮተ-ዓለም ካላቸው ጥላቻ በመነሳት የሚያራግቡት ነገር ገንቢ ለሆነ ጥናትና የሃሳብ መንሸራሸር መንገዱን ይዘጋል። መፍትሄም ለመፈልግ በጣም ያስቸግራል።

   በኢትዮጵያ ምድር የመደብለ ፓርቲ መኖር ፋይዳቢስነት!

ከዛሬው አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት አንዳንዶች የምርጫን ጉዳይ አጥብቀው ያነሳሉ። ሌሎች ደግሞ በአሁኑ የአገራችን ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ዋጋ እንደሌለው ያመለክታሉ። ይሁንና የአብዛኛው ህዝብ ጆሮ በምርጫ ላይ ያተኮረ ይመስላል።  እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ ብዙ ነገሮች መሟላት አለባቸው። ከተጠናከረ ድርጅታዊ መዋቅር ባሻገር በአንድ አገር ውስጥ የሚገኘው ብቃትነት ያለው ተቋምና የኢኮኖሚው ሁኔታ በበቂው መመርመር ያለባቸው ጉዳይ ይመስለኛል። ከዚህም በላይ በህዝቡ ዘንድ ያለው ንቃተ-ህሊናና የትኛውን ፓርቲ ለመምረጥ ያለው ግንዛቤና ፕሮግራሙን መረዳት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። በተለይም ስለመደብለ ፓርቲና ስለምርጫ አስፈላጊነት የሚያወሩ ሰዎች ከራሳቸው ሁኔታ በመነሳት እንጂ አገሪቱና ህዝባችን ካሉበት ሁኔታ በመነሳት አይደለም የጉዳዮችን አስፈላጊነት የሚያነሱት።

የመደብለ ፓርቲን መኖርና የምርጫ መካሄድን ጉዳይ በንፅፅር ጥናት መመልከቱ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። አብዛኛዎቻችን ከተሳሳተ ሁኔታና አነባበብ በመነሳት የምናስተጋባው ኢንፎርሜሽኖች ብዙ ሰዎችን ግራ እያጋባ ነው። በተለይም የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ የሚባሉትን ጽንሰ-ሃሳቦች እንደ ችግር መፍቻ ሆነው በሚቀርቡበት አገር ውስጥ በተጨባጭ የሚታዩ ህብረተሰብአዊ ችግሮችን እንዳናነብና አንድ ጠንካራ አገር ለመመስረት እንዳንችል ያደርገናል። ይህ ዐይነቱ ግንዛቤ ለምን ተፈጠረ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው። አብዛኛው ስለሊበራል ዲሞክራሲና ስለ ነፃ ገበያ የሚያወራው ፖለቲካኛ ነኝ ባይ የጽንሰ-ሃሳቦችን አፈጣጠርና ከተጨባጩ የካፒታሊስት ስርዓት ጋር ያላቸውን ግኑኝነት በሚገባ ስለማያነብና ስለማይረዳ ነው።

ለመሆኑ መቼና እንዴትስ ነው የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ መርሆች በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ብቅ ሊሉ የቻሉት? በእርግጥስ ሁለቱም ጽንሰ-ሃሳቦች በተግባር የታዩበት የካፒታሊስት አገር አለ ወይ?  የሊበራል አስተሳሰብ በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ዲስፖቲያዊ አገዛዝንና አስተሳሰብን በመቃወም፣ በተለይም ግለሰባዊ ነፃነትንና ወሳኝነትን መኖርና አስፈላጊነት በመመርመርና በማስመር የተፈጠረ አስተሳሰብ ነው። ይሁንና ግን አስተሳሰቡ ከመስፋፋቱ በስተቀር ግለሰቦች በዚህ አዲሱ አስተሳሰብ ዙሪያ ለመደራጀት የሚችሉበት የማቴሪያልም ሆነ ህብረተሰብአዊ ኃይል በጊዜው አልነበራቸውም።  በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ድረስ የመደብለ-ፓርቲ ስርዓት የተስፋፋ አልነበረም። እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ በአብዛኛዎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የፍጹም ሞናርኪዎች የሚገዙበት ዘመን ስለነበር፣ እያንዳንዱ አገር ወደ ህብረ-ብሄር እንዲሸጋገርና ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ለመገንባት በመንግስት የሚደገፍ ዕውቅ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይካሄድ ነበር። በተለይም ከሰላሳ ዓመቱ የሃይማኖት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ሆን ብለው የያዙት ወደ ውስጥ ያተኮረ አገር ግንባታ ላይ ነው። የውስጡን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የሚያስፈልግ መሆኑን የተረዱት አገዛዞች የሰውን ኃይልና ጥሬ-ሀብትንና ዕውቀትን በማንቀሳቀስ በአገራቸው ውስጥ ማንነታቸውን ማረጋገጥ መቻል ነበር ዋናው ዓላማቸው። ወደ ውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ሲገነባ ብቻ ነው  የህዝቡን የማሰብ ኃይልና የባህል ሁኔታ ማሳደግ ይቻላል ብለው የተነሱት የፍጹም ሞናርኪዎች ለካፒታሊዝም ዕድገት የማይናቅ አሰተዋፅዖ ማበርከት ችለዋል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረሰ ህብረተሰቡ እንደመደብ ገና ያላደገና የማሰብ ኃይሉም ያልዳበረ ስለነበር የተለያዩ መደቦችን ጥቅም የሚያስጠብቁ የተለያየ ስም ያላቸው ፓርቲዎች ብቅ ሊሉና ሊያድጉ በፍጹም አልቻሉም። የፓርሌሜንታሪ ሲስተም በእንግሊዝ አገር ቢኖርም ይህም በእራሱ በጊዜው የመሬት ከበርቴውን ጥቅም በሚያስጠብቁ  ኮንሰርቫቲቭ ኃይሎችና በደንብ ባልተደራጁ ግን ደግሞ እያደገ የመጣውን የከበርቴ መደብ ጥቅም እናስጠብቃለን በሚሉ ሊበራል ኃይሎች መሀከል የሚካሄድ ትግል ነበር። የኢንዱስትሪ አብዮት ከተካሄደና በአብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የካፒታሊስት ስርዓት ሲዳብርና ሲስፋፋ በመጀመሪያ ደረጃ የዓለም አቀፍ ኮሙኒስት እንቅስቃሴና የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ብቅ ማለት ይችላሉ። የማርክሲዝም ርዕዮተ-ዓለም መስፋፋትና የሰራተኛው መደብ እንቅስቃሴ ማየል እንደ ጀርመን በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ የፋሺሽት ፓርቲ እንዲወለድ አደረገ። ይህ አዲሱ ሁኔታ የኋላ ኋላ በጊዜው ብቅ ማለት የጀመሩትን ፓርቲዎች እንዳለ ደመሰሳቸው። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት መገባደድ ድረስ ዛሬ እንደምናየው ዐይነት ፓርቲዎች በጀርመን ምድርም ሆነ በሌሎች የካፒታሊስት አገሮች በደንብ የተስፋፉና እንደዛሬ የጎለመሱ አልነበሩም። ወደ ደቡቡ አውሮፓ ስንመጣ ደግሞ፣ ስፔይን፣ ግሪክና ፖርቱጋል አገሮች ውስጥ እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ፋሺስታዊ ወይም አምባገነናዊ አገዛዞች ብቻ ነበር የሰፈኑት። ወደ ጣሊያንና ፈረንሳይ ስንመጣ ደግሞ በስድሳኛውና በሰባኛው ዓ.ም የነበሩና ከፍተኛ ሚና የነበራቸው እንደኮሙኒስትና ሶሻሊስት ፓርቲዎችም ሆነ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ወይም ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎች እንዳለ ደብዛቸው ጠፍቷል። በእነሱ ምትክ ፖፑሊስትና የፋሺሽት ፓርቲዎች ብቅ ብቅ በማለት ለፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ ከፍተኛ ማነቆ እየሆኑ በመምጣት ላይ ይገኛሉ።

ለማለት የምፈልገው የመደብለ-ፓርቲ አስፈላጊነት አንገብጋቢ ጉዳይ የሚሆነው የአንድ አገር የማቴሪያል ሁኔታ ካደገና ህዝቡም በተለያየ መንገድ ሲተሳሰርና እንደማህበረሰብ ሲገለጽ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ መኖር አለበት። ከተማዎችና መንደሮች በደንብ መገንባትና በተለያየ የመመላለሻ መንግዶች መተሳሰር አለባቸው። የህዝቡ የመፍጠርና የባህል ሁኔታ መዳበር አለባቸው። የፖለቲካውና የመንግስት መኪናው ዘመናዊና ዕድገትን አራማጅ በሆነ አዲስ አወቃቀር መተካት አለባቸው። አዲስ የፖለቲካ ባህልን የሚያለማምድ የፖለቲካ ባህል፣ እነ ሚልተን ፖለቲካል ሞደርኒቲ (political modernity)ብለው የሚጠሩት ቀስ በቀስ መለመድ አለባቸው። ይህም ማለት በርዕዮተ-ዓለም ወይም ህብረተሰቡን በሚመለከቱ ነገሮች የመከራከር ባህልና የተሻለ ሃሳብ የማቅረብ ልምድ መዳበር አለባቸው። አንዱ ሌላውን የሚጠላው ሳይሆን ከእሱ ጋር ለመስራት የሚችልና በተለይም ብሄራዊ ጥቅምን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ የጋራ ስምምነት እንዲኖር ያስፈልጋል።  በሌላ አነጋገር፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ወይም መንግስት የባላይነቱን የማይጭንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የመከራከር፣ የራስን ራዕይ ማዳበርና እሱን እንደ ዕምነት ወስዶ በሱ ዙሪያ የህብረተሰቡ ችግር እንዴት እንደሚፈታ መከራከርና ወደ ውጭ ቅስቀሳ ማድረግ መለመድና እንደባህል መወሰድ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ይህ ከመሆኑ በፊት በሌለ የመደብለ ፓርቲ ዙሪያ የሚደረገው ክርክርና ስለምርጫ ማውራት አላስፈላጊና የጊዜው የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ አይደለም። ከዚህም ባሻገር ዛሬ በአገራችን ምድር ይኸኛውን ወይም ያኛውን ርዕዮተ-ዓለም አስተጋባለሁ፣ አምንበታለሁም ብሎ በመደራጀት የሚንቀሳቀስ አንዳችም ድርጅት የለም። አሉ ከተባለም ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ መንቀሳቀስና ሃሳባቸውን ማሰራጨትና ህዝቡን ማስተማር በፍጹም አይችሉም። በሌላ ወገን ደግሞ ሶሻል ዲሞክራቲክ ወይም ሊበራል ፓርቲ ነን በማለት የሚንቀሳቀሱና የየፓርቲዎቻቸው ፕሮግራምና የውስጥ ዲሞክራሲ ውይይታቸው ምን እንደሚመስል በግልጽ የማይታወቅ ድርጅት ነን ባዮች አሉ። እዚህ ውጭ አገር አልፈው አልፈው ከሚመጡ የድርጅት ተጠሪዎች ጋር ውይይት ሳደርግ ወይም ጥያቄ ሳቀርብ የማገኘው መልስ በተለይም የኢኮኖሚና የሶሻል ጥያቄዎችን አንስተው እንደማይወያዩ ነው የሚነግሩኝ። ለማንኛውም መጠሪያቸው ባደረጉት ርዕዮተ-ዓለም ያምኑበት ወይም አያምኑበት እንደሆን  በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ የለም። ማለት የሚቻለው እነዚህ የተለያየ ስምን ለጥፈው ለስልጣን የሚታገሉ ድርጅቶች የፍልስፍና መሰረታቸው ምን እንደሆን በፍጹም የሚታወቅ ነገር የለም። በራሳቸው ኃይልም የሚንቀሳቀሱና ብሄራዊ ባህርይ ያላቸው አይደሉም። አብዛኛዎቹ በአዲስ አበባ ውስጥ፣ ያውም በተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚንቀሳቀሱና ከህብረተሰቡ ጋርም ምንም ዐይነት ግኑኝነት የሌላቸው ናቸው። የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ሁኔታ፣ የቤትና ህክምና የማግኘት ጉዳይና፣ ሌሎች ሰፋ ያሉ ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማንሳት ህዝቡን በማሰተማርና፥ በመንግስትና በአገዛዙ ላይ ጫና ለማድረግ የሚችሉ አይደሉም። ባጭሩ አብዛኛዎቹ እዚያው እየኖሩ አገሪቱን ማን እንደሚያስተዳድራትና፣ የውጭ ኃይሎችን ሚና የሚከታተሉ አይደሉም። ስለሆነም በግልጽ ስለማይታወቅና ድርጅታዊ መዋቅር ስለሌለው ፓርቲ ማውራት ጊዜን ማባከንና ዕድገት እንዳይመጣ ማድረግ ነው።

ከዚህ ስንነሳ መቅደም ያለበት ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ በሁሉም አኳያ ሰፋ ያለ ውይይትና ጥናት፣ እንዲሁም ክርክር ማድረግ ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ አገራችን አሁን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንድትወጣ ከተፈለገ በብሄር ላይ ከተመሰረተ አገዛዝ ይልቅ የተለያየ ሙያ ያላቸውንና የሰለጠኑ ሰዎችን ያካተተ መንግስት መቋቋም አለበት። በዚህ ዙሪያ የተባበረ መንግስት(United Front) መፍጠርና በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ የተፋጠነ ዕድገት እንዲመጣ ሁሉም ርብርቦሹን በሱ ላይ ማድረግ አለበት። ስለሆነም በየቦታው ያሉት ብሄረሰቦችን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች በሙሉ መከልከል አለባቸው፤ ህልውና እንዳይኖራቸውም ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ ተቀዳሚው ተግባር መሆን ያለበት ጉዳይ አገርን መገንባት የሚለው መርህ ነው። ያደጉ የካፒታሊስት አገሮች፣ የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ፣ እንዲሁም የቻይና ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጡት። ኢኮኖሚው ሲያድግና አገራዊ ባህርይ ሲኖረው፣ በተለይም የሰለጠነ ባህል ሲስፋፋ አዳዲስ የህበረተሰብ ኃይሎች በመፈጠር ለፖለቲካ ባህልና ዕድገት ልዩ ዕምርታ ይሰጡታል። ስለሆነም የምርጫንና የልዩ ልዩ ፓርቲዎችን ጉዳይ በመርሳት እንዴት አድርገን ነው የሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ አገር መመስረትና መገንባት የምንችለው? በሚለው ላይ መረባረቡ ለችግራችን መፍትሄ ሊሆን ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ።

የየብሄረሰቦቻችንን  አርማ ይዘን እንታገላለን የሚሉና ክልላቸውን የሚያስተዳድሩ በመሰረቱ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች አይደሉም። ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በብሄር-አቀፍ ደረጃ መደራጀት ያለበት ሳይሆን የሚያነሳቸውም ጥያቄዎች አጠቃላይ የሆኑ የፍትህ ጉዳይ፣ ለምሳሌ የፖለቲካ ፍትህነት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች፣ ከእነዚህ ጋር የተያያዘው የነፃነት ጥያቄ መሆን አለባቸው። እንደሚታወቀው ነፃነት የሚካፈል፣ ለአንዱ ተስጥቶ ለሌላ የሚነፈግ ነገር ባለመሆኑ የብሄረሰብን አርማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጠቅላላው ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅ እንቅፋት ይሆናሉ። ስለሆነም የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ከአጠቃላዩና የአገር መገንቢያ ፖሊሲዎች ነጥሎ ማየት አይቻልም። ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያና ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ የሚከፍት በደንብ የተጠና የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ፖለቲካ በብሄረሰብ የጠባብ አመለካከት ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉም።  የብሄረሰብ እንቅስቃሴ የሚያነሳው የጭቆናንና የማንነትን ጥያቄ ስለሆነ እነዚህን አገር አቀፋዊ ሊያደርጋቸው አይችልም። የማንነት ጥያቄ የሚባል ነገር ባይኖርም የጭቆና ጉዳይ የመሳሰሉት ጥያቄዎች ከአጠቃላዩ የፖለቲካ ሁኔታና ከመንግስቱ መኪና አንፃር መታየት ያለባቸውና በሂደት መልስ ሊያገኙ የሚችሉ ናቸው። ባጭሩ የነፃነት ጥያቄና ጉዳይ በአገር ደረጃ የሚፈታና ጠቅላላውን ህዝብ የሚመለከት እንደመሆኑ መጠን መፈታት የሚችለውም ጠቅላላውን የፖለቲካ ሁኔታና የመንግስትን አወቃቀርና ከውጭ አገሮች ጋር ያለውን ትስስር እንደመነሻ አድርገን የወሰድን እንደሆን ብቻ ነው። አሁን ባለው ክልላዊ አወቃቀር በየክልሉ የሚኖሩ ህዝቦች ዕውነተኛ ነፃነታቸውን በፍጹም ሊቀዳጁ አይችሉም። በየቦታው ባለው የፖለቲካ ኤሊት የሚበዘበዙና ለዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ጥሬ-ሀብት አምራች ሆነው እንዲቀሩ የሚደረጉ ናቸው። ስለሆነም ዕውነተኛ እኩልነትንና ነፃነትን ሊያስፍኑ አይችሉም ማለት ነው። ችግሩ መታየት ያለበት ከሶስይሎጂና ከስነ-ልቦና፣ እንዲሁም ከባህል ዕድገት አንፃር እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ያለ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ አባል ነኝ የሚል እወክልሃለሁ በሚለው ኤሊት በፍጹም ዕውነተኛ ነፃነትን ሊቀዳጅ አይችልም። የጠቅላላው ህዝብ ችግር ሊፈታ የሚችለው በስርዓት በሚካሄድ የባህል እንቅስቃሴና የንቃተ-ህሊና እንቅስቃሴ አማካይነት ብቻ ነው።

ወደ ትግሬ ስንመጣ ይህ ክልል በጣም አስቸጋሪ የሆነና ዴፋክቶ የራሱን መንግስት የመሰረተና የሚዝት ነው። በእኔ ዕምነት ይህ ክልል አይ ከኢትዮጵያ መገንጠልና የራሱን መንግስት በይፋ ማወጅ አለበት፤ ወይም ደግሞ መሳሪያውን በማስረከብና ጦር ሰራዊቱን በመበተን የኢትዮጵያ የግዛት አካል መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ስለሆነም የትግሬ ሁኔታ አንድ መቋጠሪያ እስካላገኘ ድረስ የራስ ምታት በመሆን በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርግ ነው። ወያኔ የትግሬን ህዝብ እንደቁራኛ በመያዝ የሚያደርገው የተሳሳተ ቅስቀሳ ተቀባይነት ሊኖረው በፍጹም አይችልም። በሌላ ወገን የወያኔን አገዛዝ የሚቃወሙ እንደ አረና የመሳሰሉ ድርጅቶችና አንዳንድ የትግሬ ኤሊቶች እራሳችውን ከዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብና የመገለል ባህርይ መላቀቅ አለባቸው። በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንሳተፈላን የሚሉ ከሆነ እንደትግሬነታቸው ሳይሆን ነፃ አስተሳሰብና የሚያራምዱት ርዕዮተ-ዓለም ካላቸው ከሌሎች ብሄራዊ ባህርይ አለን ከሚሉ ድርጅቶች ጋር በመቀላቀል ወይም አባል በመሆን ማንነታችውን ማሳየትና መታገል ይችላሉ። በተለይም በትግሬ ክልል ውስጥ ያለው ድህነትና ረሃብ፣ የዋጋ ውድነትና የስራ-አጥነት ችግር፣ በአጠቃላይ ሲታይ በኢኮኖሚ ችግር መጎሳቆልና የነፃነት ጉዳይ…ወዘተ. ሊፈቱ የሚችሉት በወያኔ አገዛዝ ስር በመሆን ሳይሆን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሁኔታ በመነሳት ነው። ዕውነተኛ ነፃነትም ማግኘት የሚቻለው ሳይፈሩና ሳይቸሩ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ከተቀላቀሉና ከተጋቡ ብቻ ነው። አሁን ባለው የመገለለና የመሸሽ ባህርይ ዕድገትንና ነፃነትን ሳይሆን ድህነትንና የጨለማ ኑሮን ነው መጎናጸፍ የሚቻለው።

ያም ሆነ ይህ በጠቅላላው በየክልሎች ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት አዲስና የተገለጸለት የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋት አለበት። የየክልሉ አስተዳዳሪ የግዴታ ከአንድ ብሄረሰብ የወጣ መሆን የለበትም። አንድ ክልል ውስጥ ተወልዶ ያደገና ብቃት ያለው የአንድ ክልል አስተዳዳሪ መሆን ይችላል። ዋናው ነገር ክልሉን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደርና ሁለ-ገብ የሆነ ዕድገትን ማምጣት ነው ከእሱ የሚጠበቀው። አንድን ብሄረሰብ እወክላለሁ የሚል ነው አስተዳዳሪ ሊሆን የሚችለው የሚል የተፈጥሮ ህግ የለም። አንድ ሰው የአንድ ብሄረሰብ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ እወክልሃለሁ የሚለውን ብሄረሰብ ወደ ተስተካከለ ዕድገት ሊያመራው በፍጹም አይችልም። ይህ ቢሆን ኖሮማ የኤርትራ ህዝብ ወደ ጭቆና ስርዓት ውስጥ ባልወደቀ ነበር። የትግሬ ብሄረሰብም ሙሉ ነፃነቱን ተቀዳጅቶ በደስታና በብልጽግና መኖር በቻለ ነበር። ከዚህ ስንነሳ ግልጽነት የሌለው የኦሮሞ ብሄረሰብ ትግል፣ ድልን እስክንቀዳጅ ድረስ ትግሉን አናቋርጥም የሚለው አባባል ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት በፍጹም የለውም።

ለማንኛውም በአጠቃላይ ሲታይ የየክልል አስተዳዳሪዎች የአስተሳሰብ ችግር አለባቸው። በተወሰኑ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ብቻ ሰው እንዲሳተፍ ይገፋፋሉ። በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል ያለው ሚዛናዊ አካሄድ እየተመጣጠነ ሀብት እንዲሰራጭ አይደረግም። አንዳንድ አገልግሎት መስጫዎች የአንድ ከተማ ህዝብ ከሚፈለገው በላይ ተስፋፍተው ይገኛሉ። ለምሳሌ በጎንደር ከተማ የባጃጅ ብዛት ከተማዋን ማጣበቡ ብቻ ሳይሆን፣ በባጃጅ ለመጓዝ ከሚፈልገውም ሆነ ከፍሎ ለመሄድ ከሚችለው ህዝብ በላይ በከተማዋ ውስጥ ብዙ ባጃጆች ሲሽከረከሩ ይታያሉ። ለዚህ ደግሞ የከተማው አስተዳደር ተጠያቂ ነው። እንደሰማሁት ከሆነ አስተዳደሩ ሌላ የስራ መስክ ዕድል ለመክፈትም ሆነ በምን መስክ ላይ መዋለ-ነዋ ቢፈስ የስራ ቦታ የመክፈት ዕድል ሊኖር ይችላል? የሚል ጥናትና ምርምር ስለማያደርግ  በዚህ መስክ ብቻ እንዲሰማራ ለወጣቱ ብድር ይሰጠዋል። በሌላ ወገን ግን የከተማዋ ኗሪም ሆነ በአካባቢው የሚኖረው ህዝብ ብዙ የሚፈልጋቸውና በቀጥታ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ የቁሳቁስና የፍጆታ እቃዎች አሉ። በእነዚህና ሌሎች በዕደ-ጥበብና በእጅ ተሰርተው በሚቀርቡ ነገሮች ላይ መዋለ-ነዋይ ቢፈስ አዲስ የአመራረት ባህልም መማር በተቻለ ነበር።

ለማንኛውም ይህ ሁኔታ የሚያመለክተው የየክልሉና የየከተማዎች አስተዳደር አዳዲስና ለፈጠራ የሚያመቹ የተሰበጣጠሩ ሆኖም ግን ሊያያዙ የሚችሉ የኢኮኖሚ መስኮችን የማስፋፋት ኃይልና ዕውቀት የላቸውም። ስለሆነም በየክልሎችና በየከተማዎች አዲስ የሰው ኃይል ሊሰለጥን የሚችልበት ሁኔታና አዳዲስ የኢኮኖሚ መዋቅሮች የሚዘረጉበት ሁኔታ  እስካልተፈጠረ ድረስ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ ይፈጠራል። በተለይም ወጣቱ አላስፈላጊ ወደ ሆኑ ተግባራት በመሰማራት ለህዝቡ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ይህንን ነው በተለይም በአሰላ ከተማና በሌሎች የኦሮሚያ ከተማዎች፣ ለምሳሌ እንደ ጂማና አጋሮ በመሳሰሉትና፣ በባህርዳርና በጐንደር ከተማዎች የምናየው። ወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸው ትምህርትና የሙያ ስልጠና እስካላገኙ ድረስ እራሳቸውንም ሆነ ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ በፍጹም አይችሉም። ስለሆነም የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ራስን ለመከላከል በሚል ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ሚሊሽያኖችን ከማስለጠንና እርስ በእርስ ከመፋጠጥ ይልቅ ወደ አገርና ክልል ግንባታ ቢሸጋገሩ ዛሬ በጠቅላላው  በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውሶች ቀስ በቀስ መቅረፍ በቻሉ ነበር።  ከዚህ ስንነሳ የየክልሉ አስተዳደር  ያሰለጠናቸው ሚሊሺያኖችም ሆኑ ወይም ወታደሮች መበተንና ለሚሊሺያኖቹ አዲስ የስራ መስክ መፈጠር አለበት። ሁሉም ምርታማ ወደ ሆነ የስራ መስክ መሰማራት አለባቸው።  ከዚህ በተረፈ ሁሉም ክልሎች ሁሉንም ብሄረሰብ ያካተተ የአስተዳደርና የፖሊስ መዋቅር መዘርጋት አለባቸው። ኦሮሞው አማራ ክልል፣ አማራው ኦሮሞ ክልል፣ ሌላውም እንደዚሁ ሌላ ክልል ሄደው ተቀጥረው የሚሰሩበትና የመንግስት አገልጋይ የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። እስካሁን ድረስ ባለው መልክ እንጓዝ የምንል ከሆነ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት እንዲመጣ አንፈልግም እንደማለት ይቆጠራል። የገበያ ወይም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በክልል ደረጃና በየመስሪያቤቱ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦች በተሰገሰጉበት ሁኔታ ውስጥ ሊስፋፋና ሊዳብር በፍጹም አይችልም። የገበያ ኢኮኖሚ የስራ-ክፍፍልን ይጠይቃል። የሃሳብ መንሸራሸርንና የፈጠራን ጉዳይም ይሻል።  ይህ በራሱ የካፒታልንና የሰውን እንቅስቃሴ ይፈልጋል። ባጭሩ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በዐይነትም ሆነ በብዛት የሚያድገው ህዝቡ ሲቀላቀልና የመንቀሳቀስ መብቱ ሲታወቅና እርግጠኛም ሲሆን ብቻ ነው። በዚህ መልክ ብቻ ነው ብሄራዊ ሀብት ማዳበርና አንድን ህዝብ ነፃ ማውጣት የሚቻለው።

   ከብርሃን ይልቅ ሙቀት የበዛበት ፖለቲካ(More Heat than Light!)

ሚሮቭስኪ የሚባል የፊዚክስና የኢኮኖሚክስ ምሁር የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ የሚባሉ ከፊዚክስ ሞዴሎችን በመዋስ የኢኮኖሚ ቲዎሪን ያዳበሩ ምሁራንን አስመልክቶ ሲተች በማቲማቲካል ሞዴሎች ከማሽብረቅና ሰውን ከማደናበር በስተቀር አዲስና ችግር ፈች የሆነ ቲዎሪ አላዳበሩም ይላል። በእሱ ዕምነትም የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ምሁሮች መነሻ ምርት ሳይሆን የፍጆታ አጠቃቀምን በማቲማቲካል ሞዴል ለመፍታት መነሳት ሲሆን፣ ከፍጆታ አጠቃቀም በፊት ምርት እንዴትና በምን ዘዴ መመረት እንዳለበት የኢኮኖሚ መሰረተ-ሃሳብ መሆኑን ያመለክታል። በሌላ አነጋገር፣ ስለፍጆታ ከማሰብና በሱ ላይ ከመረባረብ በፊት ስለ ምርት መመረትና በምንስ ዐይነት ሁኔታና የምርት መሳሪያዎች ቅንብር እንደሚመረት ማሰብና መተንተን ያስፈልጋል። የአንድን ህብረተሰብ የሀብት መጠን የሚወሰነው በዚያው ህብረተሰብ ውስጥ በምርት መሳሪያ፣ በሰው ኃይልና በኃይል ቅንብር አማካይነት የሚመረተው ምርትና፣ ይህ ምርታዊ ክንውን በሳይንስና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተደግፎ  ምርታማነቱም ሲያድግና የሰውን ፍላጎት ማሟላት ሲቻል ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ በማቲማቲካል ሞዴል የሚያተኩረውና ከምርት ክንውን በፊት በፍጆታ አጠቃቀም ላይ(Utility Maximization) የሚያተኩረው የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ የሰውን ጭንቅላት በትክክል ነገር እንዳይጠመድ በማድረግ በውዥንብር ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ስንመጣ ህዝቡን በሚመለከተው መሰረታዊ ችግሮች ላይ ከማትኮርና ስላምና መረጋጋት እንዲሰፈን አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ህዝባችን የሚንቀለቀል እሳት በሚመስል እየተፈጀ ነው። የፖለቲካው ሁኔታ የተስፋ ብርሃንን ከማንፀባረቅ ይልቅ ህዝባችን እዚህና እዚያ በሚወራጩ አክቲቪስቶች በእሳት እየተለበለበ ነው። መሄጃና መድረሻ ያጣና በገዛ አገሩ በነፃ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብቱ ተነፍጓል። በየቦታው ፍርሃት ከመንገሱም የተነሳ ሰፊው ህዝብ ብሶቱን ወደ ውጭ አውጥቶ መናገር እንዳይችል ተደርጓል። ይህ በእንደዚህ እያለ አገሪቱ ውስጥ ሰላም የሰፈነ ይመስል ትላልቅና በቃላት ያሸበረቁ ንግግሮች ይደረጋሉ። ሁሉም በየፊናው አደናጋሪ ነገሮች በማውራት የሰፊው ህዝብ አስተሳሰብ እንዲበታተን ያደርጋል።፡

በየቦታው ያሉ የክልል አስተዳዳሪዎችና የአገሪቱ አገዛዝና መንግስት ይህንን ሁኔታና የህዝባችንን ፍርሃት እያዩ ዝም ብለው ይመለከታሉ። እንዲያውም እራሱ መንግስትና የክልል አስተዳዳሪዎች ተባባሪዎች ይመስል ቄሮ ለሚባሉ ቡድኖች ሜዳውን ልቅ በማድረግ አገሪቱን ማን እንደሚያስተዳድር  ግልጽ ያልሆነበት ሁኔታ ይታያል። ሰሞኑን በጃዋር አነሳሽነት የተቀሰቀሰው አስፈሪና አሰቃቂ ድርጊት መንግስት የሚባልና 110 ሚሊዮንን ህዝብ የሚወክል በአገራችን ምድር አለ ወይ? ብለን እንድንጠይቅ አስገድዶናል። መዓት ህዝብ ተገድሎና ህዝቡ በፍርሃት ዓለም ውስጥ እየኖረ ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይና አቶ ለማ አደጋ የደሰበትን ህዝብና ቦታዎችን እየሄዱ ከመጠየቅና ከመጎብኘት ይልቅ አባገዳዎችንና የኦሮሞ አክቲቪስቶችን ነው ሄደው መለማመጥ የጀመሩት። በእሳቸውም ሆነ በአቶ ለማ አመለካከት መቅደም ያለበት  የኦሮሞ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት እንጂ የጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም።  ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ መሪዎቻችን በምን ዐይነት ሎጂክ እንደሚመሩና እንዴትስ እንደሚያስቡ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።

ለማንኛውም  ይህ አስከፊ ሁኔታ አፍጦ አግጦ እያለና ህዝባችን በኑሮ ውድነት እየተማረረ በሚገኝበት ወቅት መንግስት ወይም አገዛዙ የህዝቡን ችግሮች ለመቅረፍ የሚችል ይመስል ብዙ ቲያትር ይሰራል፤  ሲሰራም ይታያል። ህዝቡ ራበኝ፣ ጠማኝ ሲልና በድህነት ሲማቅቅ በማክሮ ኢኮኖሚክስና በፕራይቬታይዜሽን ዙሪያ የማያስፈልግ ክረክር ይደረጋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ አባል ስለመሆኗ አስፈላጊነት እየተጠናና ሌት ተቀን በዚህ ዙሪያ እንደሚሰራ ይወራል። የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት ነው በሚለው መርህ ፈንታ ሁሉንም ነገር ገበያ ይፈታዋል በማለት አሁንም አገዛዙ የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን ምክር በመስማት ህዝባዊ ሀብት ወይም ብሄራዊ ሀብት በማይፈጥሩ ነገሮች ላይ ያተኩራል። በየጊዜው ከውጭ እየተጋበዙ የሚመጡ የታወቁ ኤክስፐርቶችና ከታወቁ የዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶች ጋር የሚሰሩ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በኤክሰፐርትነት ስም የሚሆን የማይሆን ምክር በመስጠት የፖለቲካ ኤሊቱን እያሳሳቱት ነው። በተለይም „በብዛት እየተንጋጉ የሚመጡ“ ቱሪስቶችን ሊያስተናግድ የሚችል በቂ ሆቴል ቤት የለም በማለት ገንዘብ ያለውን በምርት ክንውን ላይ ከመሰማራት ይልቅ ሆቴል ቤቶች እንዲሰራ ይደረጋል። በሆቴል ቤቶች ጋጋታና በሰው ብዛት የተነሳ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ለህዝቡ በቂ ውሃና መብራት ማዳረስ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በተለይም ከአንዳንድ አገሮች ምሳሌ ስንወሰድ ልክ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች መንግስታትም የአገራችን አዲሱ አገዛዝ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት አገሪቱ ያላትን የሰው ኃይልና ጥሬ-ሀብት ከማንቀሳቀስ ይልቅ የህዝቡ አትኩሮ በሌሎች ነገሮች ላይ እንዲጠመድ ያደርጋል። ለምሳሌ ጀርመን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በአሜሪካኖችና በእንግሊዞች የቦንብ ድብደባ አብዛኛው ከተማዎቻቸው ከሰማንያ በመቶ በላይ ወድመዋል። ህዝቡ የሚበላውና የሚጠጣው አልነበረውም። መብራትም ሆነ ማሞቂያ ማግኘት አይችልም ነበር። እናቶች የሚበሉት ነገር ከማጣታቸው የተነሳ ልጆቻቸውን ለመመገብ ድንች እንደምንም ፈልገው ካመጡ በኋላ እነሱ ልጣቹን በመብላት ለልጆቻቸው ፍሬውን ያበሏቸው ነበር። ከእንደዚህ ዐይነቱ የብሄራዊ ውርደት ለመላቀቅና በሁለት እግራቸው ለመቆም ጀርመኖች የውጭ አማካሪዎችን ምክር አልጠየቁም። በእርግጥ በነበረው የፖለቲካ ሽንፈት የተነሳ የአሜሪካኖች ተፅዕኖ ነበረባቸው። በጊዜው ወደ 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የማርሻል ዕርዳታ በመባል የሚታወቅ እንዳገኙም ግልጽ ነው። ጀርመን እንደገና ለማንሰራራትና ዛሬ ያለችበት ደረጃ ለመድረስ የማርሻል ዕርዳታ ሳይሆን ወሳኙ፣ ወሳኙ ለማደግ ያላቸው ውስጣዊ ፍላጎትና ድርጅታዊ ችሎታ ነው እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ያስቻላቸው። በመሆኑም 15 ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፈራረሱ ከተማዎቻቸውን እንደገና በመገንባት ለመነሳት ችለዋል። የፈራረሱ ኢንዱስትሪዎቻቸውን በመገጣጠምና በአዲስ መልክ በማዋቀር፣ በተለይም ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ውጭ በሚልኩት የኢንዱስትሪ ምርት መንጥቀው ለመውጣት ችለዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የውጭ ንግድ ሚዛናቸው የትርፍ ትርፍ የሚያገኝ ነው። የታወቁና የሚወደዱ መኪናዎችን በማምረት የመነጠቀ ቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። በማሺን ቴክኖሎጂ የሚወዳደራቸው የለም። አስራስድስቱም ክፍለ-ሀገሮች ወይም ፌዴራል መንግስታት በእኩል ደረጃ ያደጉ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የፌዴራል መንግስት ዋና ከተማ የጠቅላላው የጀርመን ዋና ከተማ የመሆን አቅም አለው። በሁሉም ከተማዎች ውስጥ የተወሳሰቡ የህዝብ ማመላለሻዎች ተስፋፍተዋል። ስለሆነም ይህንን ሁሉ ዕድገት ለመቀዳጀትና ብዙ የውጭ አገር ሰዎችን ለማስተናገድ የቻሉት በተከታታይ በመስራትና ስትራቴጂካሊ በማሰብ ነው። ጭቅጭቅን ሳይሆን ስራን በማስቀደምና በዕቅድ በመስራት ነው።

ወደ ሌሎች አገሮችም ስንመጣ ተመሳሳይ ሁኔታንና በራስ መተማመንን እንመለከታለን። ራሺያኖች በአንደኛውና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ከተደበደቡና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ካለቀባቸው በኋላ ጦርነቱን በድል በመወጣት ከተማዎቻቸውን እንደገና መልሰው በመገንባትና ሰፊውን ህዝብ በስራ ላይ በማሰማራትና ከድህነት በማላቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአቶም ቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ራሺያኖች እንደምዕራብ አውሮፓ አገሮች የማርሻል ዕርዳታ አላገኙም። ዕድገታቸውም በራሳቸው መተማመንና ዕውቀት እንዲሁም ጥሬ-ሀብት ላይ የተመሰረተ ነው። ቻይናዎች በ1949 ዓ.ም ድልን ሲቀዳጁ 500 ሚሊዮን ህዝብን በማደራጀትና ከረሃብ በማላቀቅ ነው ዛሬ የደረሱበት የቴኮኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቁት። ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካን ቦንብ ከተማዎቿ እንዳለ ከተደመሰሱና በጠቅላላው ኮሪያ ውስጥ አራት ሚሊዮን ህዝብ ከሞተ በኋላ ከተማዎቿን እንደገና መልሳ በመገንባት ዛሬ የባሊስቲክ ሚሳይል ባለቤት በመሆን ማንም ሊያጠቃት አይችልም። እንደዚህ ስል ስርዓቱን መደገፌ ሳይሆን ከሀፍረት ለመውጣት ያደረጉትን ጥረትና በራሳቸው ላይ መተማመናቸውን ብቻ ለማሳየት ነው።

ወደ እኛ አገር ስንመጣ የሚካሄደው ፖለቲካ የዩልኝ ፖለቲካ ይመስላል። ኃይልን የሚሰበስብና ህዝቡን በረድፍ በረድፉ እንዲደራጅ የሚያደርግ ሳይሆን የሚበታትንና በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚያደርገው ነው። በራሱ ላይ እንዳይተማመንና ነፃነት እንዳይሰማው እየተደረገ ነው። የፖለቲካው ኤሊት በቁም ነገርና በሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ ከማትኮር ይልቅ በሚሆን በማይሆን ነገር ላይ ጊዜ ያባክናል። ሁለ-ገብ ፖሊሲ አውጥቶ የተትረፈረውን የሰው ኃይልና የጥሬ-ሀብት ከማንቀሳቀስ ይልቅ በነጥብ በነጥብ በሚካሄዱ ነገሮች ላይ ብቻ በደስታ ይረካል።  ከዚህ ስንነሳ አጠቃላዩ ፖለቲካ ከብርሃን ይልቅ ሙቀት የበዛበትና የሚለበልብ ነው ለማለት እቃጣለህ። ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታና አስተሳሰብ እስካልተላቀቅን ድረስ ዕውነተኛ ዕድገት ማየት አንችልም። ስለሆነም ከሁለት ነገሮች አንዱን መምረጥ የጊዜው አንገብጋቤ ጉዳይ ነው። ወይ በትናንሽ ነገሮች ላይ ማትኮርና እየተተራመሱ መኖር፣ አሊያም ደግሞ ከውጭ ተፅዕኖ የሚያላቅቅ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ታሪክ ሰርቶ ማለፍ።

     መደምደሚያ!

በአጠቃላይ ሲታይ ህዝባችንና አገራችን ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ከመንግስቱ በሻገር በኢትዮጵያ ስም የሚነገዱና የሚምሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የአገራችንን ታሪክ የሚክዱ፣ አንድ የሚያደርገን ታሪክ የለንም በሚሉት መሀክል የፖለቲካው አየር ታምቋል። በዚህ ላይ አገሪቱ ጥራትን ሳይሆን ውዝንብርን በሚያስከትልና ህዝቡን ግራ በሚያጋቡ ኤክስፐርቶች ነን ባዮች፣ የዚህም ሆነ የዚያ ሃይማኖት ዕምነት ተከታዮች ነን ባዮች፣ የሚሆነውን የማይሆነውን እያወሩ በተለይም ወጣቱን በሚያሳስቱ ኃይሎች ከፍተኛ ውዥንብር እየተነዛ ነው። አገሪቱ ወዴት እንደምትጓዝ በቀጥታ ማወቅ የማይቻልበት ወቅት ላይ ወድቀናል። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች በአንዳች ቲዎሪና ፍልስፍና ወይም ሳይንስ ተመርኩዘው ስለማይንቀሳቀሱ በትክክል አቋማቸውን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። ቀለም የሌላቸው፣ ከፖለቲካ ወይም ከርዕዮተ-ዓለም አንፃር ሲመረመሩ እንደዚህ ዐይነቱን አቋም ነው የሚያራምዱት፣ ስልጣንም ላይ በሚወጡበት ጊዜ ይህንን የሚመስል ፖሊሲ ነው ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉት ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። ይህ ዐይነቱ ግልጽነት የሌለውና በአንዳች ዐይነት ፍልስፍና ወይም ሳይንስ የማይደገፍ ፖለቲካ የሰውን አስተሳሰብ በአየር ላይ ተንሳፎ እንዲቀር ከማድረግ በስተቀር የነፃነቱንና የዕድገቱን መንገድ ማሳየት የሚችል አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ በጣም አደገኛ የሚሆነው በውጭ ኃይሎች በመደገፍና ገንዘብ እንዲፈስላቸው በመደረግ ወጣት ኃይሎችን በጥላቻ መንፈስ የሚቀሰቅሱ ኃይሎችን መዋጋቱ ነው።

ከዚህ ሁሉ ሁላችንንም የሚያሳስበው ጉዳይ በተለይም ምሁር ነኝ የሚለው ለህዝቡ አቅጣጫ ለመስጠት የሚያስችለው ፍልስፍና ሊያፈልቅና ሊያዳብር አለመቻሉ ነው። አብዛኛው የውጭ ኃይሎችን፣ በተለይም የአሜሪካንን የበላይነት የተቀበለ ይመስላል። ከዚህ ውጭ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መወሰን አይቻልም ብሎ ደምድሟል። ይህ ዐይነቱ በራስ ላይ ዕምነት ማጣትና በውጭ ኃይሎች ላይ መተማመንን መፍጠር ለነፃነትና ለዕውነተኛ ህብረተሰብአዊና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚደረገውን ትግል እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል። እንደምናየው የምዕራቡ ድጋፍ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአገራችን ውስጥ ባለፈው 27 ዓመታት ዘራፊና አምባገነናዊ መንግስት እንዲፈጠርና ህዝባችንን እንዲጨቆንና ፍዳውን እንዲያሳይ ነው ያደረገው። አሜሪካ አንድን መንግስት የሚደግፈው አገዛዙ ጦርነት እስካካሄደለትና ህብረተሰብአዊ  ዝብርቅርቅነት እንዲመጣ ካደረገለት ብቻ ነው። ቢያንስ ቻይናዎች የተሻለ ስራ ይሰራሉ። ከምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም አሳሳችና አገር አፍራሽ ፖለቲካ በመማር አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ይሰራሉ። አሜሪካን የአፄ ኃይለስላሴ ወዳጅ በነበረበት ጊዜና፣ ህውሃትን አቅፎ ደግፎ ህዝባችንን ረግጦ እንዲገዛ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ „ይሰጥ ከነበረው ድጋፍ“  ከቻይናው ጋር ሲወዳደር ከቻይና የሚመጣው ድጋፍና ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት በብዙ እጅ የተሻለ ነው። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አካሄድ ዕውነተኛ ነፃነትና ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትን የማምጣት ኃይል የለውም። ያም ሆነ ይህ የአሜሪካን ወንጀል በግልጽ እየታየና፣ ከዚያ በሚመጣውም የኢኮኖሚ ፖሊሲና ተግባራዊነቱ አገራችንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮችም በሚታመሱበት ጊዜ ሁላችንም አሜሪካንን እንደ ነፃ አውጭና የዲሞክራሲ ብርሃን አፈንጣቂ ኃይል አድርገን ተቀብለናል።

ይህንን ሁሉ ዐይነቱን የፖለቲካ ውዥንብርና መወናበድ መቋቋም በፍጹም አይቻልም። በተለይም ሰው በግልጽ ለመወያየትና ለመከራከር በማይፈልግበት ሁኔታ ውስጥ ኃይልን መጨረስ ብቻ ነው ትርፉ። የራስን ህይውት እያበላሹ መታገልና ይህንን ሁሉ ግፊትና ቲዎሪ-አልባ አካሄድ መቋቋም በፍጹም አይቻልም። የአንድ ህብረተሰብ ትግል ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የአስተሳሰብ አንድነት(Unity of Thought) ሲኖር ብቻ ነው። የአስተሳሰብ አንድነት ሲኖርና፣ በተለይም በአሁኑ የውዥንብር ዓለም የአስተሳሰብ ጥራት ብቻ ሳይሆን ተከታታይነት ያለው የጠራ አስተሳሰብ ሲሰራ ለህብረተሰብአዊ ለውጥ የሚደረገው ትግል መልክ ሊይዝ ይችላል። ለተከታታና ጥራት ለሚኖረው ስራ ደግሞ  የማቴሪያል ሁኔታዎች መዘጋጀት አለባቸው። ሳይንሳዊና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ጽሁፎችን በተከታታይነትና ጥራትነት ባለው አቀራረብ በየጊዜው ለንባብ ማቅረብ ያስፈልጋል። ጋዜጣ ወይም መጽሄት ወይም ለዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ማስተጋቢያ የሚሆን ልዩ ዐይነት ድህረ-ገጽ ለማዘጋጀት የሰው ኃይልና የማቴሪያል ሁኔታ በበቂው መዘጋጀት አለባቸው። ይህ ሁሉ ነገር በአንድና በሁለት ሰዎች ትከሻ ላይ የሚወድቅ ሳይሆን የብዙ ሰዎችን ቆራጥና ተከታታይነት ያለው ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። ይህ ጉዳይ ደግሞ ዞሮ ዞሮ መደራጀትንና ለአንድ ዓላማ መቆምን ይጠይቃል። አንድ አገር በአክቲቪስቶችና እዚህና እዚያ በሚደረግ ንግግር አይደለም ነፃ የምትወጣው። ጥራትና ተከታታይነት ባለው ስራ እንጂ!! መልካም ግንዛቤ !!

                                                                  fekadubekele21@gmx.de