[gtranslate]

በነፃ ገበያና በሊበራላይዜሽን ስም የሚሰራው ትልቁ የታሪክ ወንጀል!

                                                             ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                            ታህሳስ 23 2021     መግቢያ

ወያኔ ስልጣን ይዞ ለ27 ዓመታት ያህል ህዝባችንን ሲያስተዳድር ሳይሆን ሲረግጥና የአገራችንን ሀብት ሲዘርፍ ይህንን ለማድረግ እንዴት ቻለ? የተጠቀመበትስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን ዐይነት ነው? ወያኔም ሆነ የተቃዋሚ ኃይሎች እንደሚሉት የዲሞክራቲክ አብዮትን በመጠቀም፣ ወይስ ስሙ የማይታወቅ ይሁንና ግን ለዘረፋ የሚያመች አገዛዝ በመመስረት? እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችንና ህዝባችንን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ውይይትና ክርክር፣ ወይም ደግሞ ጥናትና ምርምር ስላልተደረጉና ስለማይደረጉ በተለይም በነፃ ገበያ ስም የሚካሄዱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የመጨረሻ መጨረሻ አገርን የማፍራረስ ኃይላቸው ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም በተለይም በውጭ ኃይሎች ግፊት የሚካሄዱና አንድ አገዛዝ ባለማወቅ ተግባራዊ የሚያደርገው ፖሊሲ የግዴታ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን የማባለግ ኃይሉ ከፍተኛ ስለሆነ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ተብላልቶና ከአገር ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከህዝብ ፍላጎት፣ አገር ውስጥ ከሚገኘው ተፈጥሮአዊ ሀብትና የሰለጠነ የሰው ኃይል፣እንዲሁም ከኃይል አሰላለፍ ጋር ተነፃፅሮ ተግባራዊ የማይሆን ፖሊሲ የግዴታ በፖለቲካው የኃይል አሰላለፍ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚው ሂደት፣ በማህበራዊ ሁኔታ ላይ፣ በከተማዎች አገነባብ ላይ፣ በአካባቢ ሁኔታ፣ በባህልና በስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። እ.አ. በ1991 ዓ.ም  ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ ወዲህ ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲና ያስከተለውን ማህበረሰብአዊ ጉዳት አስመልክቶ በየጊዜው እየተከታተለ የሚያጠና ተቋም በሌለበት አገር በምድር ላይ የሚታዩት ማህበራዊ፣  የአካባቢ ቀውሶች፣ የተበላሹ የመንገድና የቤት አሰራሮች በሙሉ ዝም ብለው የሚታለፉ እንጂ ለምንድነው እንደዚህ ዐይነት ሁኔታ የሚታየው? ለምንስ በዚህ መልክ ይሰራል? ብሎ ምርምርና ጥናት ለማድረግ ጥረት አይደረግም። በዚህም ምክንያት የተነሳና ችግሮቹ በየጊዜው ስለማይቀረፉ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገሩ የመጡና ለአንድ ህብረተሰብ ጠቃሚ የሆኑ የአኗኗር ዘዴዎችና መተሳሰቦች ይበጣጠሳሉ። አዲስ በተፈጠረው ሁኔታ ሁሉም በየፊናው ስለሚሯሯጥ የሚጎዱት በተለይም በዕድሜያቸው ገፋ ያሉና ለመስራት የማይችሉ ሰዎች ናቸው። ይህ ሁኔታ ዛሬ አፍጦና አግጦ ያለ ጉዳይ ነው።  የዚህ ሁሉ ዋናው ችግር በአገራችን ውስጥ በተቋም የተደገፈ የጥናት ልምድ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ምሁር ነኝ ባዩም ማህበራዊና ሌሎች ህብረተሰብአዊ ችግሮችን የማንበብ ንቃተ-ህሊናው በጣም ደካማም በመሆኑ ነው። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የአካባቢ ቀውሶችን ትችታዊ በሆነ መልክ የመመልከትና ጥያቄ የማንሳት ልምድ ስላላዳበረ ዝም ብሎ ያልፋቸዋል። ስለሆነም በምድር ላይ የሚታዩት ማህበረሰብአዊ ቀውሶች በሙሉ ሰው ሰራሾች ሳይሆኑ ተፈጥሮአዊ ተደርገው ይወሰዳሉ፤ ወይም ደግሞ በደንታ ቢስነት ዝም ብለው ይታለፋሉ። አንድ ወጥ አስተሳሰብና የትምህርት አሰጣጥ በመለመዱ አንዱ ሌላውን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ደግሞ መንግስትን የመጠየቅና የመጋፈጥ ባህል የላቸውም። ስለሆነም ጥያቄ መጠየቅ፣ መተንፈስ፣ መተቸትና መከራከር እንደወንጀል  ይወሰዳሉ። በተለይም ደግሞ መንግስትን ወይም አንድን አገዛዝ መተቸት ማለት የኢግዚአብሄርን ቃል እንደመጣስ በሚቆጠርበት አገር ሁሉም አንገቱን ደፍቶ እንዲሄድ ይገደዳል። ለዚህ ዐይነት የተወላገደ አስተሳሰብ በአገራችን ምድር በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ዕውቀት(Scientific Knowledge) ባለመስፋፋቱና ቲዎሬቲካል ዕውቀት(Theoretical Knowledge) የአንድን ህብረተሰብ የተወሳሰበ ችግር የመመርመሪያና መፍቺያ መሳሪያ መሆኑን ካለማወቅ የተነሳ ነው። ምክንያቱም ካለሳይንሳዊ ቲዎሪ አንድን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ስለማይቻል ነው።

እዚህ የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችም ሆነ አሜሪካን፣ ካፒታሊዝም የሰውን ህይወት በሚቆጣጠርበት ዓለም ውስጥ አንድ ዐይነት አመለካከት ብቻ ያላቸው የኢኮኖሚ የምርምር ተቋማት የሉም። የታላላቅ ኩባንያዎችንም ሆነ የሌሎችን ካፒታሊስቶችን ጥቅም የሚያስጠብቁና በእነሱ የሚደገፉ የኢኮኖሚ ተቋማት ሲኖሩ፣ የሰራተኛውንም ጥቅም የሚያስጠብቁም እንደዚሁ በሰራተኛው የሙያ ማህበርና በሌሎች የሚደጎሙ ትንሽ ግራ መልክ አስተሳሰብ ያላቸው የምርምር ተቋማት እንደዚሁ አሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሙሉ ሙሉ በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ የሚመሩና ከማርክሲዝም አንፃር የኢኮኖሚውን ሁኔታ የሚመረምሩ፣ የሀብትን ክፍፍል የሚያጠኑና በመንግስት ላይ ጫና የሚያደርጉ ድርጅቶችም አሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ድህነትንና የሀብት ክፍፍልንና ክምችትን በሚመለከት፣ ችግሩን ከሶስይሎጂ አንፃር በመመርመርና  መፍትሄ በማቅረብ ማህበራዊ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የሚያድርጉና በመንግስት ላይ ጫና የሚያደርጉ አሉ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን አንድ ህብረተሰብ እየተወሳሰበ ሲመጣ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን መንግስት ብቻውን ስለማይፈታቸው፣ ወይም ደግሞ የገበያ ኢኮኖሚ መፍታት ስለማይችል የግዴታ በተቋማት በተደገፈ መልክና በመደጋገፍ ችግሮቹ የሚቃለሉበት ዘዴዎች ይፈጠራሉ። በንቃተ-ህሊና መዳበር፣ በተቋማት መስፋፋትና፣ በመጻህፍት ቤቶች እንደልብ መገኘትና፣ እንደዚሁም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የአካባቢን ቀውሶችና የጥሬ-ሀብትን ጉዳይ አስመልክቶ በየጊዜው አዳዲስ ጽሁፎችና መጽሀፎች ስለሚታተሙ  እየተወሳሰቡ የሚመጡ ችግሮችን የማየትና የመወያየት ልምድ አለ። ስለሆነም በየጊዜው የሚነሱት ጥያቄዎች የመጭውንም ትውልድ የሚመለከቱና፣ ለመጭው ትውልድም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ጥሎ ላለማለፍ መሞከርና ስትራቴጂ መቀየስ በአውሮፓ የካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ እንደ ባህልና ልምድ ተቀባይነትን አግኝቷል ማለት ይቻላል። ይህንን በሚመለከትና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ዕድገት የሚባለው ነገር በሚመጡት ሃምሳና መቶ ዓመታት በዚህ መልክ ሊቀጥል ስለማይችል በምን ዘዴ ተከታታይነት ያለው፣ የጥሬ-ሀብትን በተቆጠበ መልክ የመጠቀም ጉዳይና የአየር ሙቀትንና መበከልን መቀነስ በሚሉት ነገሮች ጥናቶችና ክርክሮች ይካሄዳሉ።

እንደኛ ወዳለው ምንም ዐይነት ምሁራዊ ክርክር በሌለበት፣ አንድ ወጥ የኢኮኖሚ ቲዎሪ ብቻ በሚሰጥበት አገርና፣ ተማሪዎችም የአገራቸንን ተጨባጭ ሁኔታ((Socio-economic formation) በደንብ እንዲያውቁ ትምህርት በማይሰጥበትና ጥናት በማይደረግበት አገር ውስጥ ባለፊት 30 ዓመታት በነፃ ገበያ ስም የተካሄደውና የሚካሄደው ፖሊሲ የግዴታ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ  ሁኔታና ምክንያቱንም ለማወቅ የሞከረና የሚሞክር በፍጹም የለም። ፖሊሲው ተግባራዊ መሆን ከጀመረበትና፣ አገራችንም የግሎባላይዜሽን አንዱ አካል ልትሆን ከበቃችበት ጊዜ ጀምሮ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ እንደሚታየውና ዛሬም ቢሆን ቢል ጌትና ኤሎን መስክ እንደሚያሳዩን በፈጠራና በታታሪነት ሳይሆን በዘረፋ ሀብት በሚከማችበት አገር ውስጥ በቀላሉ የብልግና ኢንዱስትሪ መስፋፋቱ ከስርዓቱ ወይም ከኢኮኖሚ ፖሊሲው ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በአገራችን የሚታየው መዝረክረክና የብልግና ኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ እንዲሁም የጥቂቶች መንደላቀቅ በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም የሚታይና በተለይም ወጣቱን ለዕፅ ሱስ የዳረገ ነው።  ከዚህ በመነሳት፣ በተለይም ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህንን  በሚመለከት ባለፈው ሳምንት ያሰራጨሁትን ጽሁፍ አስመልክቶ አንዳንድ ያልተብላሉ፣ ግንዛቤ ውስጥ ያልገቡና የታለፉ ጉዳዮች ስላሉ የግዴታ  ግልጽ ለማድረግ ተገድጃለሁ።

                      የታሪክን ሂደት ያላገናዘበ የነፃ ገበያ አራማጆቾ ሰበካ!

አብዛኛዎች የኢኮኖሚክስ ትምህርትን የሚማሩና በዚህ የሚመረቁና የዶክትሬት ዲግሪም ሆነ ከዚያ በላይ ማዕረግ ያላቸው የሶስተኛው ዓለም አገር ተማሪዎች፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን እንዳያዉቁም ሆነ እንዳይማሩ የተደረገው ካፒሊዝም የተጓዘበትን የዕድገት ደረጃና ዛሬ እንዴት ዓለምን ለመቆጣጠር የቻለበትን ሁኔታ ነው።

የካፒታሊዝምን አፃናነስ በሚመለከት፣ ማርክስም ሆነ ሌሎች ከማርክሲዝም ጋር በቀጥታ የማይገናኙ ተማራማሪዎች  ስለአስተዳደጉና እንዴት እየተወሳሰበ መምጣት እንደቻለ በሰፊው ተመራምረዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ካፒታሊዝም ታስቦና ታቅዶ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሳይሆን ከብዙ ጊዜ የህብረተሰብ ክንውንና ግጭት በኋላ ዛሬ እንደምናየው በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመደገፍ የሚካሄድ የምርት ክንውን ነው። በተለያዩ ጊዜያቶች በጻፍኳቸው ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ለካፒታሊዝም መፀነስና ማደግ የባህል ለውጥ፣ በተለይም ደግሞ የአስተሳሰብ ለውጥ ዐይነተኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ነው። በሌላ ወገን ግን ፈላስፋዎችም ሆነ ሳይንስቲስቶች፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የሶስይሎጂና የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች ሰለ ለውጥ አስፈላጊነት ሲያወሩም ሆነ ለውጥ ከተደረገም በኋላ ምርምር ሲያደርጉ እንደዚህ ዐይነት ስርዓት መቋቋም አለበት ብለው እንዳላስተማሩ መገንዘብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ከሁለት መቶና ሶስት መቶ ዓመት በኋላ የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ ነው። በሌላ ወገን ግን አንድ ማህበረሰብ የግዴታ በሞራልና በስነ-ምግባር፣ እንዲሁም ጥበባዊ በሆነ መልክ መደራጀትና መገንባት እንዳለበት በመሀከላቻው ስምምነት ነበረ። በተለይም መንግስት የሚባለው ፍጡር ጥበባዊና ሞራላዊ መሆን እንዳለበትና፣ ፍትሃዊ አገዛዝን የግዴታ በማስፈን ማህበራዊ ግጭቶች ሊቀንሱ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸተ እንዳለበት አስተምረዋል።  ስለሆነም የፈላስፋዎችም ሆነ በጊዜው የሳይንቲስቶች ዋናው ምርምርና አስተሳሰብ የሰው ልጅ ራሱ ከሚፈጥረው የጭቆና ስርዓትና ተፈጥሮም ከምታደርስበት ጫናና የጨለማ ኑሮ ያለው አማራጩ መንገዱ ጭንቅላትን ወይም አዕምሮን ማደስና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ነው። በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ተፈጥሮን መቆጣጠርም ሆነ በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን በመመራመር ወደ ጠቀሜታነት መለወጥ የሚቻለው ከሚለው በመነሳት ነው። ፈላስፋዎችም ሆነ ሳይንቶስቶች ስለዘመናዊነት፣ በተለይም ስለፖለቲካ ዘመናዊነት(Political Modernization) ሲጽፉና ሲያስተምሩ ለዕድገትና ለነፃነት ዋናው ጠንቅ መንግስትና የመንግስት መኪናን የጨበጡት ፖለቲከኛ ነን ባዮች መሆናቸውን በመረዳታቸው ነው።  ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የተሟላ ዕድገት እንዲመጣ፣ በህዝብ ዘንድ ስምምነት እንዲኖርና ማንኛውም ግለሰብ በአርቆ-አስተዋይነት እየተመራ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን እንዲወጣ ከተፈለገ የግዴታ ፖለቲካዊ መሻሻል ያስፈልጋል። መንግስትም አይ በፈላስፋዎች ወይም ደግሞ በፈላስፋዎች በሚመከሩና ቁጥጥር በሚደረግባቸው ፖለቲከኞች መመራት አለበት። በጊዜው በነበሩ የፈላስፋዎች ዕምነት ፖለቲካና ስነ-ምግባር አንድ ላይ ተያይዘው መሄድ ያለባቸውና ማንኛውም ፖለቲከኛ ይህንን ማሟላት እንዳለበት ግንዛቤ ውስጥ የተገባ ነበር።

ያም ሆነ ይህ ካፒታሊዝም በአነሳሱ በተሰበጣጠረ መልክ እየዳበረ የመጣ ቢሆንም፣ ከኢንዱስትሪ አብዮትና ከህብረ-ብሄር(Nation-State) መስረታ በኋላ ግን ሁኔታው እየተለወጠ መምጣት ችሏል። በመጀመሪያ ደረጃ በጊዜው በአውሮፓ መንግስታት መሀከል የነበረው ፍኩክር መንግስታትን የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ አስገደዳቸው። በተለይም ንቁ የሆኑ(Active Forces)የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍና በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን(Infant Industries) በታሪፍና ታሪፍ ነክ ባልሆኑ ነገሮች መከላከል የየመንግስታቱ ዋና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነበር። ከዚህም በላይ ወደ ውጭ የሚወጣውን የተፈበረከ ምርት ማሳደግና የአገርን የውስጥ ገበያ ማስፋፋትና ማዳበር ሌላው ዐይነተኛ የየመንግስታቱ ፖሊሲ ነበር። ስለሆነም የአውሮፓ መንግስታት ሆን ብለው የያዙት ወደ ውስጥ ያተኮረ(Inward-Looking Strategy) የአገር ውስጥ ገበያ የሚዳብርበትን አመቺ ሁኔታዎች መፍጠር ነበር። ተቋማትን መገንባትና የባቡር ሃዲዶችን መዘርጋት፣ የተሰበጣጠረው ህዝብ ተሰባስቦ እንዲኖር ማድረግ፣ በዚህም አማካይነት የስራ-ክፍፍል የሚዳብርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነበር። ይህም ማለት በአፍላው ወቅት ለካፒታሊዝም ማደግ የየመንግስታት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የመንግስታትት ሚና በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ውስጥ በፍጹም አይሰጥም፣ ወይም ተማሪዎች እንዲማሩት አይደረግም።

በጊዜው ቀስ በቀስ እያለ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ እየዳበረ ሲመጣ በዘመኑ ብቅ ብቅ ያሉት እንደ አዳም ስሚዝ የመሳሰሉት ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ያነሱት የነበረው ጥያቄ፣ መንግስታት በተለይም በውጭ የኢኮኖሚው ላይ የሚያደርጉት የዕገዳ ፖሊሲ መነሳት እንዳለበት ነው። በእነ አዳም ስሚዝና በእነ ሪካርዶ አስተሳሰብ በየአገሮች ውስጥ የተለያየ ተፈጥሮኢዊ ሀብት ስላለና፣ በዚህም አማካይነት የስራ-ክፍፍል ሰለሚኖር የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው ከውጭ የጥሬ-ሀብትን በንግድ አማካይነት ማምጣት ሲቻል ብቻ ነው የሚል ሲሆን፣ ቀስ በቀስ ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ የየመንግስታቱ ሚና እየቀነሰ ሊመጣ ቻለ። በእነስሚዝም ዕምነት ይህ ዐይነቱ በአገሮች መሀከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ሌሎች ኋላ-ቀር አገሮችንም እንዲያድጉ አመቺ ሁኔታ ሲፈጥርላቸው፣ በዚያው መጠንም ባህላዊ ለውጥን ማምጣት ይችላሉ የሚል ነው። የስሚዝ አካሄድ የነፃ ገበያ በዚያው መልክ ሊቀጥል እንደሚችል በማሰቡና፣ ጤናማ ጎኑን ብቻ ከማየት የተነሳ በመሆኑ የነፃ ገበያ አራማጆችና የኋላ ኋላ በተለይም በጥሬ-ሀብት ቅርምት ውስጥ የተሳተፉ የአውሮፓ መንግስታት ዋናው ዓላማ  የስራና የፈጠራ ባህልን ማስፋፋት ሳይሆን የየአገሮችን ባህልና ተቋማት ማውደም መሆኑን ጠጋ ብሎ ሊያጠና ዕድል አላጋጠመውም።  በተለይም የእሱ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ወደ ተወሳሰበ የካፒታሊዝም ዕድገት፣ ለምሳሌ ወደ ኦሎጎፖሊዝምና ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ሊያመራ እንደሚችልና በዓለም አቀፍ ገበያና በጥሬ-ሀብት ቅርምት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ አላስገባም። ይህም ማለት የካፒታሊዝም ዕድገትና በሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ያለው ኋላ-ቀርነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን በፍጹም አልተገነዘበም። በሌላ  ወገን ግን አዳም ስሚዝ ስለነፃ ገበያ በሚያወራበት ጊዜ የነፃ ገበያን ዕድገት ከሞራልና ከእሴት ውጭ ነጥሎ በፍጹም አላየም። በእሱ አመለካከት በሰው ልጅ መሀከል መተሳሰብ ስላለ የግዴታ እያንዳንዱ በገበያ ውስጥ የሚሳተፍ በገበያ ውስጥ ሊቆይ የሚችለው የተወሰኑ ሞራላዊ ግዴታዎችን ካሟላ ብቻ ነው። ይኸውም ማንኛውም አምራች ኃይልና ነጋዴ ምርቱ በተከታታይነት እንዲሸጥለትና ደንበኛም ላለማጣት ከፈለገ የግዴታ ሀቀኛ መሆን እንዳለበት ያስተምራል። ከዚህ በላይ ስሚዝም ሆነ ሌሎች የጊዜው ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው፣ 1ኛ) የስራ-ክፍፍል ሲኖርና በዚህም አማካይነት የንግድ ልውውጥ ሲካሄድ ብቻ ነው። 2ኛ) ማኑፋክቸር ወይም የማሽን ኢንዱስትሪ መኖርና በዚህ አማካይነት የተለያዩ ምርቶች መመረት የግዴታ የገበያ ኢኮኖሚን ዕድገት ያፋጥናል። 3ኛ) የገበያው ስፋት ለገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው። 4ኛ) ገበያ ግልጽ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር ዛሬ በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደሚታየው ግልጽ ያልሆነና መጭበርበር የበዛበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም። እነ አዳም ስሚዝ ለአንድ አገር ዕድገት በማሺንና በማኑፋክቸር ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ አስፈላጊ መሆኑን ቢያወሱም፣ የመንግስትን ሚና ሙሉ በሙሉ ውድቅ አላደረጉም። በተለይም ተቋማትን በመገንባት፣ በትምህርትቤቶችና በጤንነትና እንዲሁም በኢንፍራስትራክቸር ላይ ሚና እንዳለው አለፍ አለፍ አድርገው አውስተዋል። ከዚህም ባሻገር የሰው ልጅና የአንድ አገር ህይወትና ዕድል በኢኮኖሚ ብቻ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት በፍጹም አላስተማሩም። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ማህበረሰብና አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሞራላዊ፣ ጥበባዊና በሌሎችም ነገሮች የሚገለጽ ነው። ለሌሎች የኢንላይተንሜንት ምሁራንም ይህ ጉዳይ ግልጽ ነው።

ይሁንና የካፒታሊዝምን የተወሳሰበ ዕድገትና በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተካሄደውን ዕልክ አስጨራሽ ምሁራዊ ክርክር ያልተከታተሉ ጥራዝ ነጠቅ ኢኮኖሚስቶች ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከእነ ዓለም ባንክ ጋር በመመሰጣጠር፣ እነ አዳም ስሚዝም ሆነ ማርክስ፣ እንዲሁም ደግሞ እነ ኬይንስ ያላስተማሩትንና በተግባርም ያለተረጋገጠውን እንደኛ ባለው ደካማና ደሃ አገር ላይ በመጫን ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል፣ የስነ-ልቦናና የባህል  መከስከስ፣ እንዲሁም ደግሞ የአካባቢ ውድመት እንዲመጣ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እነሱ ባረቀቁትና ተግባራዊ እንዲሆን በሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ጤናማና ብሄራዊ ባህርይ ያለው መንግስትና አገዛዝ ሳይሆን ዘራፊ መንግስትና(Predatory State) አገር አውዳሚ መንግስትና አገዛዝ፣ እንዲሁም አምባገነናዊ ወይም ፋሺስታዊ መንግስት እንዲመሰረት ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ በዚህ ዐይነቱ የካፒታሊዝምን ዕድገትና አሰራር ያላገናዘበ ፖሊሲ እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ዕውነተኛ ፈጣሪና ታታሪ፣ እንዲሁም ከሚያገኘው ትርፍ ውስጥ እየመላለሰ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ገንዘቡን የሚያፈስ የከበርቴ መደብ የሚፈጠር ሳይሆን ቶሎ ቶሎ ገንዘብ ለማግኘት ሲል በአልባሌ ነገሮች ላይ የሚሰማራ አቀባባይ የከበርቴ መደብ ነው ብቅ የሚለው።

ከዚይህ ስንነሳ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በእነ ዓለም ባንክ፣ ባጭሩ በዓለም ኮሚኒቲው ረቆ እንደኛ ያለው አገዛዝ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስም ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማንኛውም የካፒታሊስት አገር ተግባራዊ ያልሆነ ነው። አንደኛውም የካፒታሊስት አገርም ሆነ፣ በኋላ የተነሱት እንደነ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ታይዋን፣ ዛሬ ደግሞ ቻይና የመሳሰሉት በቴክኖሎጂ ዕድገት መጥቀው የተነሱ አገሮች በሙሉ  የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን ፖሊሲና ምክር በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ አይደለም እንደዚህ ዐይነቱን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊጎናጸፉና፣ ወደ ውስጥ ደግሞ በተለያየ ኢፍራስትራክቸርና በባቡር ሃዲድ የተያያዙ ከተማዎችንና የውስጥ ገበያን ማሳደግ የቻሉት። ባጭሩ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፖሊሲ ሳይሆን ተራ ማጭበርበር ነው። በአገራችን ውስጥ እንደምናየው አንድ አገር በአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አቅጣጫ ድምጥማጧን የሚያጠፋና ወንበዴ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል እንደ አሸን እንዲፈለፈል የሚያደርግ ነው። ባጭሩ የባህልን ውድመትና የስነ-ልቦናን መከስከስ የሚያስከትል ነው።

          ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያላገናዘበና የህብረተሰብን ፍላጎት ማዕከላዊ ያላደረገ

                   የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ ፖሊሲ ሊቆጠር አይችልም!!

ማንኛውም ሰው አሞት ሃኪም ቤት በሚሄድበት ጊዜ ሃኪሙ ለህመምተኛው መድሃኒት ከማዘዙ በፊት ለምን እንደመጣ መጠየቅ አለበት። ከዚህም በመነሳት ሃኪሙ ህመምተኛውን ከበሽታው ጋር የተያያዙ ነገሮችንና፣ እንደ አመጋገብና ስፖርት መስራት፣ አልክሆል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ፣ እንዲሁም ሌሎች ልማዶች ይኑሩት አይኑሩት ይጠይቀዋል። በቤተሰቡ ውስጥ እንደዚያ ዐይነት በሽታ እንዳለው ይጠይቀዋል። ጥያቄዎችን ከጠየቀና ተገቢ መልስ ካገኘ በኋላ አስፈላጊውን ምርምራ ያደርግለታል። ሃኪሙ በሽታውን ለማከም የማይችል ከሆነ በቂ ምርምር እንዲደረግለት ልዩ ምርመራ የሚደረግበት ቦታ ወይም ሆስፒታል ይልከዋል። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ሃኪም በቂ ምርምራ ሳያደርግና እርግጠኛ ሳይሆን ለህመምተኛው አንድ መድሃኒት አያዝለትም። ወይም ደግሞ ከዚህ በፊት ለአንድ ታካሚዬ ያዘዝኩለት መድሃኒት ይህ ስለሆነ ለአንተም ይህ ይሆናል በማለት ከበሽታው ጋር የማይጣጣምና በሽታውን  ሊፈውስ የማይችል መድሃኒት በፍጹም አያዝለትም። ይህ ከሆነ ደግሞ ከበሽታዬ እፈወሳለህ፣ ጥሩ ሃኪም አገኘሁ ብሎ የመጣ ታማሚ ከበሽታው ከመፈወሰ ይልቅ እየባሰበት ስለሚሄድና ምናልባትም የታዘዘለት መድሃኒት ሌላ ተጨማሪ አሉታዊ ሁኔታ የሚፈጥርለት ከሆነ የመሞቻው ጊዜ ይፋጠናል ማለት ነው።

ወደ ህብረተሰብም ስንመጣ እንደዚሁ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ማህበረሰብና አገር ከትውልድ ትውልድ የተጓዙበት የአመራረት ስልትና ባህላዊ የአኗኗር ዘዴ አለ። በዚህም የተነሳ በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ተቀርጾ የሚቀር አስተሳሰብ አለ።  ከዚህም በላይ የምርት ግንኙነትና የምርት ኃይሎች የሚባሉ ነገሮች አሉ። የዕድገታቸውን ወይም ያሉበትን ሁኔታ መመርመር በተለይም ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ለመንደፍ ያመቻል። በተጨማሪም የመንግስት መኪናና አወቃቀር፣ የመንግስቱን መኪና የጨበጠው አገዛዝ የመንፈስና የዕውቀት ሁኔታ፣ የመንግስትን ሚናና በዚያው አገር ውስጥ በምርት ሂደት ውስጥና በንግድ የሚሳተፉትን የንቃት ወይም የትምህርት ደረጃ፣ የስራ-ክፍፍል መኖርና አለመኖር ጉዳይ፣ የገበያውን ስፋትና ግልጽነት ጉዳይ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ የሚመረት ወይም የማይመረት መሆኑን…ወዘተ. …ወዘተ.  ማጥናት ያስፈልጋል። ሌላው አንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ የሚካሄድበት ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ባህላዊ እንደመሆኑ መጠን ኢኮኖሚው ስነ-ልቦናን ከማጠንከር፣ ብሄራዊ ነፃነትን ከማስከበር አንፃር፣ እያንዳንዱን ግለሰበ እንደ ነፃ ዜጋና እንደህብረተሰቡ አካል ከማጎልመስ አኳያ እየተገመገመ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሁሉ መጠናት አለበት። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በቦታና በጊዜ ውስጥ የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን ስለከተማዎችና ሰለመንደሮች አገነባብና ሁኔታ፤ እንዲሁም ስለ ኢንፍራስትራክቸር ጉዳይ በበቂውና በጥልቀት መጠናት አለበት፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ሁሉም አገሮች የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያስፈልጋቸዋል፣ ወይም ማንኛውም አገር የግዴታ የማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ አለበት ተብሎ በጭፍን ተግባራዊ የሚደረግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚሉት ነገር የተፈለገውን ውጤት አያመጣም። የዚህ ዐይነቱ የገበያ ኢኮኖሚ ዋና ዓላማው የአንድን ህዝብ ፍላጎት ማሟላት ሳይሆን  ዋና ዓላማው የገበያ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ነው የሚባል ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም መዝረክረክና ውንብድና የህብረተሰቡ መለዮች ይሆናሉ ማለት ነው። ቢያንስ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ ከብራዚል እስከ አርጀንቲና ድረስና በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ተደግፈውና ተጭነው ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ልቦናና ባህላዊ ቀውሶች ነው ያስከተሉት። ፖሊሲዎቹ ከየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የተነደፉ ባለመሆናቸውና ችግር ፈቺ ሳይሆኑ ችግር ፈጣሪ የሆኑና ያለው የተበላሸ የአሰራር ሁኔታ የባሰውኑ እንዲበላሽ ሁኔታዎችን ያመቻቹ ናቸው።  በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ የግዴታ ገበያ እንደ ተቋም አስፈላጊ የሆነውን ያህልና፣ በአንድ ህብረተሰብም ውስጥ የስራ-ክፍፍል የመኖሩ ጉዳይ እንደተፈጥሮ ህግ ተደርጎ ቢወሰድም፣ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የነፃ ገበያ ሰበካና ዓለም አቀፋዊ መሆኑ ጉዳይ በፍጹም ተፈጥሮአዊ አይደለም ወይም የተፈጥሮ ህግ አይደለም። ማንኛውም አገር ራሱን በፈለገው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መንገድ ማደራጀት ይችላል። በነፃ ገበያ ስም የዓለምን ህዝብ ፍላጎት በአንድ የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ ለመገደብ መወሰን የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው። ምክንያቱም ተፈጥሮ ራሷ ልዩ ልዩ አትክልቶችና እንሳስት፣ እንዲሁም ኢንሴክቶችና ሌሎች ነገሮች ሲኖሯትና እንክብካቤም ስታገኝ ብቻ ነው ሚዛናዊነቷና ጠብቃ ልትዘልቅ የምትችለው።  እንደዚሁም አንድ ህብረተሰብ ጤናማና ሚዛናዊ ሊሆን የሚችለው ልዩ ነገሮች ሲመረቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግረው የመጡ የአቀቃልና የአሰራር ሁኔታዎች ሲሻሻሉና ሲጠበቁ ብቻ ነው። በልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጹና ለጭንቅላት መዳበር ወሳኝ የሆኑ ባህል ነክ ነገሮች ሲስፋፉና ስነ-ምግባርም ሲካተትበት አንድ ህዝብ በተሟላ መልክ የማሰብ ኃይል ይኖረዋል። ትላንትና ዛሬ፣ ዛሬና ነገ የተዛዛዙና ተከታታዩ ትውልድም የሚረከበው ቁም ነገር እንዳለና አንድ ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ ሊቆይ የሚታሰብ ከሆነ እንደዚህ ዐይነት በልዩ ልዩና ጠቃሚ ነገሮች ይተሳሰራል።  የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን የኢኮኖሚ ፖሊሲና አካሄድ ስንመለከት የየአገሮችን ባህልና የጠቃሚ የሆኑ የአኗኗር ስልቶች እንዳሉ በማውደም በአንድ ዐይነት የአመጋገብ ስልትና ገንዘብ በማኘት መተካት ነው።  የዓለምን ህዝብ አመጋገብ በሃምበርገርና በኮካላ በመተካት በየአገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጤንነት ቀውስ እንዲከሰት ማድረግ ነው።

ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ስንነሳ የእነ ዓለም የገንዘበ ድርጅትና የእነ ዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመጀመሪያ ደረጃ ፖሊሲ አይደለም። ምክንያቱም ፖሊሲው የአንድን አገር የምርት ሁኔታ የሚያሳድግ፣ የአገር ውስጥ ገበያን የሚያዳብርና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ኃይሎች እንዲሆኑ ማድረግ ሳይሆን፣ አንድን አገር ለውጭ ገበያ ክፍት በማድረግ በዕዳ መተብተብ፣ የንግድ ሚዛኑን ማዛባት፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ማራገፊያ ማድረግና፣ የመጨረሻ መጨረሻ መንግስትን ጨቋኝ በማድረግ፣ በተለይም ሰፊውን ህዝብ ገለልተኛ በማድረግ አቅመ-ቢስ እንዲሆን ማድረግ ነው። ስለሆነም የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የእነ ዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በተለይም፣ ጥንታዊ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች((Classical Economic Theories) በሚባሉት፣ በኢንስቲቱሽናል የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና በኬይንስም የሚደገፍ አይደለም። ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት ፖሊሲው መነሻ የሚያደርገው የየአገሮችን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይሆን ሊሆን ይችላል ከሚለው ግምትና ሁሉም አገሮች መከተል ያለባቸው፣ የነፃ ገበያን የተፈጥሮ ህግ አስመስሎ በመነሳትና በመንግስታት ላይ ጫና በማድረግ ነው። የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ የዓለም ባንክ ለፖሊሲያቸው እንደመነሻ አድርገው የሚወስዱት ከየመንግስታቱ ከሚቀርቡላቸው የስታትስቲክስ ቁጥሮች ለምሳሌ ስለበጀት፣ ስለኢምፖርትና ስለ ኤክስፖርት፣ ስለ ዕዳና አንድ አገር ከውጭው ዓለም ጋር ስላላት የንግድ ግኑኝነት በመነሳት እንጂ በምድር ላይ ከሚታየው ሁኔታ  አይደለም። እነዚህም ስለድህነትና ስለ ስራ-አጥነት፣ ምን ምን ዐይነት ኢንዱስትሪዎች እንዳሉና፣ ምን ነገሮችስ እንደሚመረቱ፣ ስለ ትናንሽና ስለ ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች መኖርና አለመኖር፣ በአጠቃላይ ሲታይ ጠቅላላው ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስልና፣ በኢንዱስትሪዎች መሀከል ስላለው ትስስር(Linkages)፣  ምንስ ዐይነት አወቃቀር አለው?  ከሚሉት በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች በመነሳት አይደለም። ሌላው ደግሞ የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ የዓለም ባንክ  መነሻ አድርገው የሚወስዱት ጠቅላላውን ሁኔታ በመገምገም ሳይሆን፣ ከአንድ ሁኔታ ብቻ በመነሳት ነው የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብለው የሚደነግጉት። ስለሆነም እንደመንግስት መኪናና የመንግስትና መኪናን የሚቆጣጠሩት እንደ ተሰጡ(as given) ወይም መሻሻል እንደማያስፈልጋቸው አድርገው ነው ፖሊሲ የሚባለውን ነገር የሚያረቁት። ይህ ዐይነቱ የሳይንስ ዘርፍ ኤምፕሪሲዝም ወይም ፖዚቲቭ ሳይንስ በመባል ሲታወቅ፣ በነገሮች መሀከል መተሳሰርና ግኑኝነት እንደሌለ አድርጎ ነው የሚወስደው።  በሌላ ወገን ደግሞ የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመረምር የመንግስት መኪና ከጨቋኝ ባህርይው መላቀቅ ወይም ዲሞክራሲያዊ መሆን፣ የሰለጠኑና የተቀላጠፉ ተቋማት(Institutions) መኖር ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ እንደቻሉ ነው። ካፒታሊዝም በራሱ ውስጥ ባለው የቴክኖሎጂ ዕድገት መፋጠን የተነሳም የግዴታ የየመንግስታትን መኪና እንዲቀላጠፉና አብረው እንዲጓዙ ለማድረግ በቅቷል። ምክንያቱም በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚቻለው ከውስጥ የተቀላጠፈና ከማንኛውም ተንኮል የፀዳ የመንግስት መኪናና አገዛዝ ሲኖር ብቻ ነው። ይሁንና ግን ማንኛውም በመንግስትም ሆነ በግለሰብ ካፒታሊስቶች አንድ ፕሮጀክት ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የግዴታ ሰፊና ጥልቀት ያለው ጥናት መካሄድ አለበት። እንደ ፕሮጀክቶች ዐይነት፣ ለምሳሌ ትልቅ የባቡር ጣቢያ ወይም የአውሮፕላን ጣቢያ ሊሰራ ከታቀደ የተደራጁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ያላቸው የሲቪል ማህበራት ጣልቃ በመግባት ተግባራዊ የመሆኑንና ያለመሆኑን ጉዳይ ያጠናሉ። ለምሳሌ ከአውሮፕላን በረራ ጋር ሊፈጠር የሚችል የሰውን መንፈስ የሚረብሽ ጩኸት፣ የአካባቢን ጉዳይና አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ሲሰራ በአካባቢው መፈናቀልን ያስከትል አያስከትል እንደሆን…ወዘተ. እነዚህ ነገሮች በሙሉ ከተመረመሩና ችግር የማይፈጠር ከሆነ ብቻ ነው አንድ ፕሮጀክት እንዲሰራ ፈቃድ ማግኘት የሚችለው። ይህም የሚያሳየን ካፒታሊዝም በተራ ስግብግብነት ላይ ብቻ ተመስርቶ ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን፣ የግዴታ ቁጥጥርም እንደሚደግበት ነው።

ለማንኛውም አንድ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መነሻ አድርጎ መነደፍ ያለበት የየአገሩን ተጨባጭ ሁኔታ በማንበብ ብቻ ነው። ተጨባጭ ሁኔታዎች ሳይነበቡና ሳይተነተኑ የሚነደፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በምድር ላይ የሚታዩትን ችግሮች፣ ለምሳሌ እንደ ድህነትና ስራ-አጥነት፣ እንዲሁም ደግሞ ሚዛኑን የሳተ የሀብት ክፍፍል የባሰውኑ  እንዲባባስ ከማድረግ በስተቀር ችግሩን ሊፈታቸው በፍጹም አይችልም። ከዚህም በላይ አንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲነደፍ ዋና ዓላማው መሆን ያለበት የገበያ ኢኮኖሚን ተግባር ማድረግ ሳይሆን የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) ማሟላት ነው። አንድ ህዝብ ወደ ስራ ዓለም ውስጥ ለመሰማራት መብላትና መጠጣት አለበት። መኖር አለበት፤ ለዚህ ደግሞ ቤት ያስፈልገዋል። ከዚህም በተጨማሪ የማሰብ ኃይሉ እንዲጨምርና ማንነቱን እንዲገነዘብ መማር አለበት። ልጆቹንም ትምህርትቤት የመላክ ዕድል እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣  ሲያመው ሊታከም የሚችልበት በአካባቢው እንደ ፖሌ ክሊኒክ የመሳሰሉ የህክምና ጣቢያዎች ያስፈልጉታል። እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች አብራሃም ማስሎው በሚባለው ይሁዲ አሜሪካዊና የሰብአዊነት ስነ-ልቦናን ዕውቀት ባዳበረው ምሁር ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው በነበሩ የኢኮኖሚ ምሁራንም እንደነ ሃይንሪሽ ፔሽ በመሳሰሉት የረቀቀና መንግስታትም መከተል እንዳለባቸው የተሰበከ ነው። ስለሆነም ነው በአውሮፓ ምድር በተለይም፣ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምክንያት የተነሳ ኢኮኖሚያቸውና ከተማዎቻቸው የወደሙባቸው፣ እንዲሁም ኢንፍራስትራክቸሮቻቸውና ልዩ ልዩ ተቋማት እንዳሉ የፈራረሱባቸው መንግስታትና አገሮች በመጀመሪያ ቅድሚያ የሰጡት ለስፊው ህዝቦቻቸው መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ነው። የፈራረሱ ቤቶችን መልሰው በመገንባት ለህዝቡ መጠለያ መስጠት ነው። እንደ መብራትና ማሞቂያ የመሳሰሉትን መጠገንና በበቂው እንዲዳረስ ማድረግ ነው።  ቀሰ በቀስም ተቋማትን በመገንባት ኢኮኖሚው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ በመደገፍ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው። ለእዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአውሮፓ መንግስታት የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን ምክር በፍጹም አልጠየቁም። በራሳችው ኢኮኖሚስቶችና ተቁማት ብቻ ነው አገሮቻቸውን መገንባት የቻሉት። በ1929 ዓ.ም ትልቁ የኢኮኖሚ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ እነ ፕሬዚደንት ሩዘቤልትም የተከሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በጊዜው የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ቀውስና ያስከተለውን እንደ ስራ-አጠነት የመሳሰሉትን መዘዞች ገበያው ይፈታዋል ብለው አይደለም እጃቸውን አጣጠፈው የተቀመጡት። በመንግስት የተደገፈና ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን በማቋቋም ነው ችግሩን ሊቋቋሙና ሊፈቱት የቻሉት። ስለሆነም ነው በጀርመን በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ 80% የሚሆኑት ቤቶችና ተቋማት፣ ኢንፍራስትራክቸር፣ መብራትና ውሃ ማከፋፈያ፤ ኢንዱስትሪዎች… ወዘተ. ከፈራረሱ በኋላ በተቀነባበረና በመንግስት ጣልቃ ገብነት 15 ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ጠቅላላውን አገራቸውን መገንባት የቻሉትና የውጭ አገር ሰዎች እየመጡና እየተጋበዙ እንዲሰሩና ቤተሰብ እንዲመሰረቱ አመቺ ሁኔታዎችን የፈጠሩት። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የየመንግስታት ዋና ተግባር አገርን በተሟላ መልክ መገንባት ሳይሆን ሆን ተብሎ የተያዘው ፈሊጥ አገርን ማፈራረስ፣ እሴቶችን መበጣጠስና የህዝብን መንፈስ አዳክሞ አገርን ለውጭ ወራሪዎች አመቻችቶ መስጠት ነው። ይህ ጉዳይ በመንግስት ላይ ብቻ የሚሳበበ ሳይሆን ምሁር ነኝ በሚለውም ላይ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው ጭንቅላታችን በሁሉም አቅጣጫ ያልዳበርና፣ ስለአገርና ስለህዝብ ያለን ስሜት በጣም የደከመ መሆኑን ነው;፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሰው የሚለው ትርጉም ያልገባን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳችንም ሰው መሆናችንን ያልተገነዘብን መሆኑን ነው። በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ተኩል በተራው ህዝባችን ላይ የሚደረገው ቅጡን ያጣ አሰቃቂ ድርጊትና፣ ወያኔ የከፈተው ጦርነትና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ መንግስት የሚባለው ፍጡር የተከተለው አደገኛ አካሄድና በተለይም በአማራውና በአፋሩ ህዝብ ላይ የደረሰው ዕልቂትና የከተማዎችና የንብረት መፈራረስ ሰው መሆናችንን እንድጠራጠር አስገድዶኛል።  ለመሆኑ በህዝብ ላይ እንደዚህ ዐይነት ግፍ እየተፈጸመ፣ በመስፋፋትና በበላይነት መንፈስ እየተሳከሩ በልቶ ያልጠገበ ህዝብ ግፍ ሲደርስበት ዝም ብሎ እያዩ ስለብልጽግና  ወይም ስለኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊነት ማውራቱ ትርጉሙ ምን እንደሆን ስለማይገባኝ ነው።

ያም ሆነ ይህ አገዛዙ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ምሁር ነኝ ባይና በድሮው ዘመን ማርክሲስት ነኝ እያለ ሲያስቸግረን የነበረው ሁሉ የያዘው ፈሊጥ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን ምክርና ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም በማለት ነው። ባጭሩ የአንድ አገር መንግስትና ምሁር ዋና ተግባርና ዓላማ አንድን አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመመርኮዝ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ሳይሆን በንግድ አማካይነት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለው በማመን ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጥገኛ ከመሆን ሌላ አማራጭ የለንም።  ስለሆነም የእነሱን ምክርና ቡራኬ እየተከተልን አገርን ማፈራረስ ነው ዋናው ተግባራችን እያሉ ነው ይነግሩን የነበረው። ከሳይንስና ከህብረተሰብ ህግ ውጭ የሆነ አስተሳሰብና አገርንና ባህልን የሚያወድም የተሸናፊዎች አስተሳሰብ ነው ማለት ነው።  በቀጥታ እንደዚህ ብለው ባይነግሩንም በተጨባጭ ይህንን ዐይነቱን አስተሳሰብ ነው የሚያራምዱት። ስለሆነም ነው ወያኔ ስልጣን ላይ ወጥቶ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲያደርግና ዛሬ እንደምናየው ሁኔታ ሲፈጠር ዝም ብለው የተመለከቱት ከዚህ ዐይነቱ ትችታዊ ካልሆነ አስተሳሰብ በመነሳት ነው። ይህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ክፍተት የሚመነጨው ደግሞ የኢኮኖሚን መሰረታዊ ዓላማ ካለመረዳት የተነሳ ብቻ ሳይሆን አንድ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ካለመረዳት ነው።

                 የነፃ ገበያው ፖሊሲና ሊበራላይዜሽን ያስከተሉት አሉታዊ ውጤቶች!

በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ከውጭ የሚመጡ ፖሊሲዎችን ካለምንም ጥርጣሬና ሳይንሳዊ ምርምር ዝም ብሎ መቀበል ነው። ተግባራዊ ሲሆንም ሊያስከትል የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖም ሆነ ውጤት የማጥናትም ሆነ የመተንተን ልምድ አለመኖሩ ለአደጋ አጋልጦናል። በተለይም በዚህ በኩል ያለው ምሁራዊ ክፍተት አንድ መቋጠሪያ ወይም መፍቻ እስካላገኘ ድረስ አገራችንን እንደ ህብረተሰብና እንደማህበረሰብ የመገንባቱም ሆነ የማቆየቱ ጉዳይ መረሳት ያለበት ነው። ምክንያቱም የአንድ አገር ዕድል ሊወሰን የሚችለው፣ ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣሁት ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት  ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ወይም ባለመገንባት ነው እንዳልኩት፣ ስለ ኢትዮጵያና ስለአንድነቷ መኖርና መቀጠል፣ ስለኢትዮጵያዊነት በምናወራበት ጊዜ ከህዝባችን ኑሮ መሻሻል ውጭ ነጥሎ ማየት እጅግ አደገኛ ነው። በድህነት ዓለም ውስጥ የሚማቅቅና ማንም የሚዘባነንበትን ህዝብ ስለኢትዮጵያዊነት አስር ጊዜ ቢዘመርልትና ቢተረትለት ምንም ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በጠንካራ ኢኮኖሚ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ግንባታ፣ ከመሰረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ጋር መያያዘ ያለበት ጉዳይ ሲሆን፣ እያንዳንዱም ዜጋ እንደ ነፃ ዜጋ መታየት ያለበትና ካለምንም ምክንያት በፖሊሶች የማይታሰርና በፍርድቤት የማይጉላላ ከሆነ የዚያን ጊዜ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማውራት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያዊነት፣ በማቴሪያል ሁኔታዎች መሻሻል የሚረጋገጥና በመንፈስም ጥንካሬና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን በመቀበል የሚገለጽ መሆን አለበት።

ያም ሆነ ይህ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ረቆ ወያኔ ተግባራዊ ያደረገውና የዛሬው አገዛዝም የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን መሰረተ-ሃሳብ የሚጻረር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የዓለም የገንዘብ ድርጅት መመሪያው በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንኳ የሚደገፍ አይደለም። ምክንያቱም በጥንታዊውና በዘመናዊ የኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ መሰረት አንድ አገር ገንዘቧን ከዶላር ጋር መቀነስ አለባት፣ መንግስት ሁሉንም ነገር ለገበያው መልቀቅ አለበት፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሀብቶችንም ለግል ባለሀብቶች መሽጥ አለበት፣ ሁሉንም ነገር ሊበራላይዝ አድርግ የሚል ስለሌለ ነው። የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ ተቀጥሮ በሚሰራው ሰራተኛና በሚያገኘው ገቢ በአንድ በኩል፣ በሌላው ወገን ደግሞ ሰራተኛው ከሚያገኘው ገቢ ውስጥ እንደገና ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ ስለሚያፈሰው ገንዘብና በዚህም አማካይነት ስለመዋዕለ-ነዋይ ሁኔታ ይነግረናል። ከዚህም በላይ በቁጠባና በመዋዕለ ነዋይ መሀከል ያለውን ግኑኝነት ብቻ ሳይሆን፣ አምራቾች ከገበያ ላለመውጣት ሲሉ ስለሚከተሏቸው ስትራቴጂዎች፣ ስለሚተክሏቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ስለሚያመርቷቸው ምርቶችና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የገበያ ኢኮኖሚ እንደደም ዝውውር  እንዴት እንደሚሰራ ያሰያናል። ይህም ማለት በማምረት፣ ገቢ በማግኘትና በፍጆታ መሀከል(Production, Distribution and Consumption) መተሳሰር ካለና የሰራተኞችም ገቢ ከግሽበት መጨመር ጋር እየተመጣጠነ የሚያድግ ከሆነ የሰራተኛው የመግዛት አቅምም(Buying Power) ይጨምራል። በዚህ መልክ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ የግዴታ ውስጣዊ-ኃይል ይኖረዋል።

ይሁንና ግን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው  የኢኮኖሚክስ ትምህርት ሰለካፒታሊዚም ኢኮኖሚ አፀናነስና አስተዳደግ፣ እንዲሁም ውስጣዊ አሰራር የሚነግረን ነገር የለም። በሁለተኛ ደረጃ፣ በአሰሪዎችና በሰራተኛው መሀከል ያለውን ግኑኝነት አይነግረንም። በተጨማሪም ሰራተኞች በስራ መስክ ላይ ስላላቸው ሁኔታና ሚና በፍጹም የሚለን ነገር የለም። የአንድን አገር ኢኮኖሚ በአቅራቢዎችና በጠያቂዎች መሀከል ሊኖር የሚችል ግኑኝነት አድርጎ ነው የሚወስደው። ስለዚህም በገበያው ውስጥ የሚሳተፈው፣ 1ኛ) የተሟላ መረጃ ወይም ኢንፎርሜሽን አለው፣ 2ኛ) አቅራቢው ትርፍን ለማካበት፣ ተጠቃሚው ደግሞ ጥቅሙን ለማሳደግ የሚሯራጥ ነው የሚል ነው። የመጨረሻ መጨረሻ  በዚህ ዐይነቱ ግኑኝነትና አማካይነት ሁሉም ሰው ተጠቃሚ ይሆናል ይለናል። በገበያ ላይ የሚሳተፉት በሙሉ ነፃ ተወዳዳሪዎች ስለሆኑ ሁሉም የመደራደር ኃይላቸው እኩል ናቸው ይለናል።

ለማንኛውም ወደነ ዓለም አቀፍ የገንዘበ ድርጅት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ስንመጣ ላይ በሰፊው የዘረዘርኩትን ለኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ-ሁኔታዎችና ተራ የኢኮኖሚክስ መሰረተ-ሃሳቦች የሚፃረር ነው። ምክንያቱም ከረጅም ጊዜ አንፃር በምርት፣ በስራ አማካይነት ገቢን በማግኘትና በዚህም አማካይነት ሊኖር የሚችለውን የፍጆታ ሁኔታ ከመጀመሪያውኑ ከስሌት ውስጥ ስለማያገባ ነው።  በአንድ አገር ውስጥ ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው አሰሪዎች የስራ-መስክ ሲከፍቱና ሲያመርቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሰራተኛው ራሱ የተመረቱትን ዕቃዎች ገዝቶ ለመጠቀም የሚያስችለው በቂ ደሞዝ ሲያገኝ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በተከታታይ የሚመረተው ምርት መሸጥና መለወጥ አለበት። የተመረተው ምርት ሲሸጥና ጠቀሜታ ላይ ሲውል አምራቹ እየመላለሰ ያመርታል። ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይታያል። ከዚህ ስንነሳ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወደ ውስጥ ምርት በተከታታይነት እንዳይመረትና፣ ተከታታይነት ያለው የቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። ፖሊሲው እንዳለ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ በጣም ደካማና የተሰበጣጠረ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች ውስጥ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የማምረት ኃይልን ያዳክማል። ያለውን የገበያ ክፍተት ለማሟላት ሲሉ ነጋዴዎች ከውጭ ዕቃዎችን እንዲያመጡ ይገደዳሉ። በዚህ ምክንያት የተነሳ የአገር ወስጥ ገበያ ሊያድግ አይችልም። በገፍ ከውጭ በሚመጣው ዕቃም የተነሳ የንግድ ሚዛኑ ይዛባል። ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ደግሞ አብዛኛዎች የቅንጦት ስለሆኑ የህዝብን ፍላጎቶች የሚያሟሉ አይደሉም። በሌላ ወገን ደግሞ በሊበራላይዜሽን ስም የአገራችን ገበያ ክፍት ከሆነ ጀምሮ በማደግ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የሚያዳክሙ ተመሳሳይ ምርቶች መግባታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ጥራት በሌላቸው ዕቃዎችና ልብሶች የተነሳና የችርቻሮ ገበያ በመስፋፋቱ ገበያው ግልጽነት እንዳይኖረው ለመደረግ በቅቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚገቡትም ምርቶች ሳይመረመሩ የሚገቡ በመሆናቸው በተለይም ምግብ ነክ የሆኑ እህሎችና የቅባት ዘይቶች ከፍተኛ የጤንነት ቀውስን ለማስክተል በቅተዋል።

ከዚህ ዐይነቱ እጅግ የተሳሳተና ኢ-ሳይንሳዊ ሁኔታ በመነሳስት ነው በየአገሮች ውስጥ የነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት እየተባለ በመንግስታት ላይ ጫና የሚደረገው። ይኸኛው አካሄድ የተቀደሰውና የእግዚአብሄሩ መንገድ ስለሆነ ይህንን የሚቃወም የእግዚአብሄርን ቃልና ህግ የጣሰ በማስመስል አስፈላጊው ዕርምጃ ይወሰድበታል። ስለሆነም ማንኛውም ደካማ አገር በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና በእነ ዓለም ባንክ የረቀቀውንና የተደነገገውን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። እነዚህም፣ 1ኛ) የአገርን ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር መቀነስ(Devalue)፣ 2ኛ)ገበያውን ከመንግስት መዳፍ ስር ማላቀቅ፣ 3ኛ) ገበያውን ልቅ ማድረግ(liberalize)፣ 4ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ ሀብቶችን መሸጥ(Privatization) … ወዘተ. … ወዘተ. እነዚህ በሙሉ ተግባራዊ ከሆኑ የነፃ ገበያ ዕውን ይሆናል ይለናል። ሁሉም የህበረተሰብ ክፍል ደስተኛ ይሆናል ይላል። እንደ ኢትዮጵያ ያለችውም አገር የዓለም ማህበረሰብ አካል በመሆን በስልጣኔ ጎዳና ወደፊት ትገሰግሳለች በማለት ከሃቁ የራቀ ነገር ይነግረናል። እነዚህ ፖሊሲዎች አንድ በአንድ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ እንደሚነገረን ሳይሆን ገንዘቡ በመቀነሱ የተነሳ የግዴታ የዋጋ ግሽበት ይፈጠራል። ምክንያቱም ከውጭ የመለዋወጫ ዕቃዎችንም ሆነ የጥሬ-ሀብቶችን ለማስመጣት የሚፈልጉ በአዲሱ የገንዘብ ልውውጥ አማካይነት የተነሳ አንድ ዶላር ለመግዛት ከድሮው ጋር ሲወዳደር የበለጠ መክፈል ስላለባቸው ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የማምረቻ ዋጋ ይጨምራል። የማምረቻ  ዋጋ ሲጨምር ደግሞ ምርቱም ገበያ ላይ በሚሸጥበት ጊዜ ዋጋው ይወደዳል ማለት ነው። ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የተደረገው የገንዘብ ቅነሳ ከፍትኛ የዋጋ ግሽበትን ያስከተለውና ህዝብን ያስመረረው። የንግድ ሚዛን መዛባትና የዕዳ ማደግና ከውስጥ ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀም መለመድ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ውጤቶች ናቸው። እነዚህ አሉታዊ ክስተቶችና የኢኮኖሚ መዛባቶች በተከታታይ ባወጣኋቸው ጽሁፎቼ ላይ በዝርዝር ተቀምጠዋል። ይሁንና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ከሰላሳ ዓመት በፊት ወያኔ እንደዚህ ዐይነቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ብሎ ጫና ሲያደርግ፣ የተነሳው  ደርግ ስልጣን ላይ ባለበት ዘመን ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ መዛባት አለ፣ ስለሆነም ይህ ዐይነቱ መዛባት በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መስተካከል አለበት ወይም ወደ ሚዛናዊነት መምጣት አለበት በማለት ነው። ከሰላሳ ዓመት በኋላ ግን በአገራችን ውስጥ ያለው መዛባት በኢኮኖሚው መስክ ብቻ ሳሆን በሁሉም አቅጣጫ የሚታይ ነው።

ለማንኛውም እነዚህ እንዳሉ ሆነው፣ በአብዛኛዎቻችን ውስጥ ግንዛቤ ያላገኙት ባለፉት 27 ዓመታ ከኢኮኖሚው ፖሊሲው ተግባራዊ ከመሆን ጋር ተጓትተው የመጡ የባህል ውድመቶች፣ የስነ-ልቦና መፈረካከስ፣ የአካባቢ መቆሸሽና በሰው ጤንነት ላይ ያስከተለው ጉዳት፣ በብሄራዊ ነፃነት ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ የመንግስቱ መኪናና አገዛዙ ወደ ዘራፊነት መለወጥ፣ ውንብድናና መስፋፋት፣ መካካድና የመጨረሻ መጨረሻ መገዳደል፣… ወዘተ. ወዘተ. እነዚህ የባህል ውድመቶች በሙሉ ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጠሩና ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትኖርና ህዝቦቿ እንዳይከበሩና፣ በአጠቃላይ ሲታይ እንድንናቅ ያደረጉ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ስላልተጠኑና ዝም ብለውም ስለሚታዩ የመባለጉ መጠን ስር እየሰደደና በቀላሉ መፍትሄም ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ከዚህም በላይ ጥንታዊዎችን ሃይማኖቶች፣ ማለትም የኦርቶዶክስን ሃይማኖትና የእስልምናን ሃይማኖቶች የሚቀናቀኑ ሌሎች በተለይም የገንዘብ ማግኛና የሰውን መንፈስ ማደንዘዣ ሃይማኖት መሰል ነገሮች እንደ አሸን ለመፍለቅ በመቻላቸውና፣ ህዝብን ከማስተማር ይልቅ አሳሳች በመሆናቸው ሰፊውን ህዝብ ግራ እንዲጋባና አቅጣጫውን እንዲስት አድርገውታል። አንድ እግዚአብሄርና አንድ ክርስቶስ ካለ የዚህ ሁሉ ሃይማኖት ጋጋታና ትርጉሙስ ምን እንደሆን ለመረዳት በጣም ያስቸግራል። ይህንን ብንተው እንኳ ራሳቸው ሰባኪዎች ከየት ገንዘብ በማግኘት ነው የሚንደላቀቁት? ለመሆኑስ ቀረጥ ይከፍላሉ ወይ? በምርት ክንውንና በፈጠራስ ላይ ይካፈላሉ ወይ? ማህበረሰብአዊና ህብረተሰብአዊ አስተዋፅዖአቸውስ ምንድነው? እንደሚታወቀው ዕድሜው ከአስራስምንት ዓመት በላይ የሆነ ሰው ሁሉ ጤናማ እስከሆነ ድረስ የአገርን ሀብት በማዳበር ውስጥ መሳተፍ አለበት። ባጭሩ መስራት አለበት። በምርት ክንውን፣ በፈጠራና በንግድ ክንውን ውስጥ መሳተፍ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው እያንዳንዱ ግለሰበ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ የሚችለው። ዝም ብሎ ከዚህም ከዚያም ገንዘብ በማግኘት ተጠቃሚ የሚሆን ህብረተሰቡን የሚጎዱ ነገሮችን ነው የሚያስፋፋው። ባጭሩ መንግስት እነዚህን ነገሮች የመከታተልና ገደብ የማሲያዝ ግዴታ አለበት። ሀዝቡን ከአደጋ መከላከል አለበት።

እነዚህን ነገሮች ትተን ወደ ሊበራላይዜሽን ወደሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ስንመጣ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ ባጭሩ የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው አስተሳሰብ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ታሪካዊ ነው። ምክንያቱም ሊበራላይዜሽን የፖለቲካ ሊበራሊዝም ከመስፋፋቱና የነቁ ኃይሎች ከመዳበራቸው ወይም ከመፍለቃቸው በፊት ስላልታየ ነው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ የተፀነሰው በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ሲሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ በጊዜው የነበረውን ጨቋኝ አገዛዝ ወይም ዲስፖታዊ አገዛዝን በመቃውም የፖለቲካ ነፃነት መኖር አለበት ከሚለው በመነሳት ነው።  በተለይም የግሪክን ፍልስፍናና የአንትሮፖሎጂ ጥናቶች የተመራመሩ የእንግሊዝና የጀርመን ፈላስፋዎች አንድ ማህበረሰብም ልክ እንደ ተፍጥሮ እየተወሳሰበና በስራ-ክፍፍል እየተደራጀ ስለሚመጣ የተሻለ ለማደግ የግዴታ የነፃነትን ብርሃን ማግኘት እንዳለበት ለመገንዘብና የኋላ ኋላም ለማስተማር ችለዋል።  ምክንያቱም አትክልቶችና ሌሎች አዕፅዋት በደንብ ሊያብቡና ሊያፈሩ የሚችሉት አስፈላጊውን ንጥረ-ነገሮችና ውሃ ሲያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ የፀሀይ-ብርሃንንም ሲያገኙም ነው። የሰውም ልጅ በአስተሳሰቡ እንዲጎለምስ ከተፈለገ ከጭቆናዊ አገዛዝ ተላቆ የተሟላ ነፃነትን መጎናፀፍ አለበት። በመሆኑም አንድ አገዛዝ ወይም ዲስፖታዊ አመለካከት በሰፈነበት አገር ውስጥ የሰው ልጅ የመፍጠር ኃይሉ ይቀጭጫል።  እግዚአብሄር የሰጠውን የማሰብ ኃይል ለመጠቀም ስለማይችል እንደ እንስሳ ለመኖር ይገደዳል። ስለሆነም ግለሰብአዊ ነፃነት ለማሰብና ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ነው በማለት ነው የዲስፖታዊ አገዛዝን አጥብቀው የታገሉት። በተግባርም እንደታየው ቀድሞ የሰብአዊነት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የከበርቴው ሊበራዚም ተግባራዊ ሲሆኑ ዕውቀት ራሱም የመስፋፋትና የመዳበር ዕድል ማግኘት ቻለ። ትችታዊ አመለካከትና አገላለጽም ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር ተያይዘው መበልጸግ ቻሉ። ይህ በራሱ ቀስ በቀስም ህብረተሰብአዊ ለውጥን ማምጣት ቻለ። ዝም ብሎ የሚነዳ ህዝብ ሳይሆን፣ ጥያቄዎችን የሚጠይቅና የሚከራከር፣ እንዲሁም አማራጭ ሃሳብ የሚያፈልቅ ህብረተሰብአዊ ኃይል ሊፈጠር ቻለ።

ወደ ዓለም የገንዘብ ድርጅቱና የዓለም ባንክ የሊበራላይዜሽን ፅንሰ-ሃሳብና ውትወታ ስንመጣ ግን ይህንን የታሪክ ሂደት ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን በተሳሳተ መልክ በኢኮኖሚው መስክ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ይህንን እንቀበል ብንል እንኳ  እንደሚነገረን በሊበራላይዜሽን አማካይነት ከውጭ ቴክኖሎጂ በፍጹም ሊመጣ አይችልም። ኢኮኖሚው ሊበራላይዝድ በሚሆንበት ጊዜ የውጭ ኢንቬስተሮች የሚሰማሩት ኢኮኖሚውን በሚያሳድግ መስክ ላይና የስራ-መስክ በሚፈጥር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሳይሆን፣ በአበባና ተመሳሳይ ምርቶች ላይ ብቻ ነው። ለብሄራዊ ሀብት ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ዕድገት በማያመቹ መስኮች ላይ ነው ማለት ነው። ይህ ይህ ዐይነቱ የሊበራላይዜሽን አስተሳሰብና አገዛዞች ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጫና ማድረግ የውጭ ኃይሎች እንደልብቻው በመግባት የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ አመቺ ሁኔታን እንዲፈጠርላቸው በማሰብ ነው። ህወሃት ለ27 ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ በዚህ ዐይነቱ የሊበራላይዜሽን ፖሊሲ አገራችንን ወደ ብልግና መስክ ከመለወጡ በስተቀር በተለይም የወጣቱን መንፈስ የሚያዳብሩ፣ ንቁ ዜጋ የሚያደርጉትና የመፍጠር ችሎታውን የሚያሻሻሉ እንደቤተ መጻህፍቶችና የስፖርት ተቋማትን፣ እንዲሁም የሙያ ማስልጠኛ ቦታዎች የመሳሰሉትን ለማስፋፋት አልቻለም። መጽሀፍ በማንበብ ብቻ ነው የዕውቀትን አድማስ ማስፋት የሚቻለው። ቤተ መጻህፍቶች እንደልብ በማይገኙበት አገር የሰው የማንበብ ፍላጎት በፍጹም አይኖረውም። የሚያደላውም ጭንቅላትን በማያዳብሩ እንደመጠጥ ቤቶች በመሳሰሉት የመዝናኛ ቦታዎች ነው። ለዚህ ነው አንዳንድ ሰዎች መጽሀፍ አሳትመው 115 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርበት አገር ከሶስት ሺህ በላይ መጽሀፎችን ማሳተምና መሸጥ የማይችሉት። በእነዚህ ዐይነቶች ተቋማትና በዕውቀት መስፋፋት ምትክ የወያኔ አገዛዝ ሆን ብሎ የተያያዘው የውጭ አገር ቱሪስቶችንና ኢንቬስተሮችን ለማስደሰትና ለማዝናናት ሆቴልቤቶችንና መደነሻ ቦታዎችን  ነው ያስፋፋው፤ ወይም እንዲስፋፉ የፈቀደው። የውጭ አማካሪዎችን የእነዚህን መስፋፋት ነው ሲገፋፉና ሲያማክሩ የነበረው።  ምክንያቱም የሚያነብና እያወቀ የሚሄድ ህዝብ ጥያቄዎችን ስለሚጠይቅና ራሱንም ስለሚችል የግዴታ በተለይም የወጣቱ  መንፈስ ባልባሌ ነገሮች መያዝ አለበት። እየተማረና እያወቀ የሚሄድ ትውልድ የመፍጠር ችሎታውም ስለሚዳብር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አይ ይኮርጃል፣ አሊያም ደግሞ ይፈጥራል። ስለሆነም ሊበራላይዜሽንን የሚሰብኩ እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የመሳሰሉት፣ በአጭሩ የዓለም ኮሚኒቲው የሚባለው የሚፈልጉት መንፈሱ የተሳከረና በብልግና ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሳተፍን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው። ስለዚህ ነው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለይም የኢኮኖሚውንና የፖለቲካ ኤሊቱን መንፈስ በመሰለብ እንደፈለጋቸው ለማድረግ የቻሉት። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው ድፍረት በተሞላበት መንገድ ጫና የሚያደርጉብን።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ቴሌና መብራት፣ እንዲሁም የአየር መንገድ የመሳሰሉትን የተወሰነ ድርሻ መሸጥ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ሊያስከትል የሚችለው መሻሻል የለም።  ለውጭ ከበርቴዎች፣ በመሰረቱ ዘራፊዎች ድርሻ መሸጡ የቴክኖሎጂ ልውጥጥን ወይም ሽግግርን አይመጣም። ለምሳሌ ቴሌ የተወሰነው ድርሻ ቢሸጥ የሞባይል ገበያ ይስፋፋል። ሞባይል ደግሞ ከውጭ የሚመጣ ነው። ባጭሩ አገሪቱ የምርት ክንውን የሚካሄድባትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚታይባት ሳይሆን ወደ ተራ ሸቀጣ-ሸቀጥ ማራገፊያነት ነው የምትለወጠው። የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የመሳሰሉት የካፒታሊስት አገሮች ተጠሪዎች ስለ ነፃ ገበያ አስፈላጊነት ሲያወሩ አገሮችን በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መዳፍ ስር ለማምጣትና የየአገሮችን ጥሬ-ሀብት ለመቀራመትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሁለ-ገብ ዕድገት እንዳይመጣ ለማድረግ የወም በሩን ለመዝጋት ነው። አገሮችን ማዳከምና ለዝንተ-ዓለም ደሃ ሆነው እንዲቀሩ ማድረግ ነው። አንድ አገር ራሷን እንድትችል የሚያደርጋና የቴክኖሎጂ ባለቤትና ፈጣሪ እንድትሆን የሚያስችላት ሳይሆን ለብዙ ዓመታት ደሃና ጥገኛ ሆና እንድትቀር የሚያደርጋት ነው

ይህ በእንደዚህ እንዳለ ሰሞኑን የሚወራው ወሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት ቢሊዮን ዶላር($ 5 ቢሊዮን) ከአዲስ አበባ 34 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ቦታ በአፍሪቃ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የአውሮፕላን ጣቢይ ለመስራት እንዳሰበ ወይም ዕቅዱ እንደተጠናቀቀና በቅርብ ጊዜ መሰራቱ እንደሚጀምር ነው። የሚነሳው ጥያቄ አገራችን አሁን ባለችበት የፖለቲካ ሁኔታና አብዛኛው ህዝባችን በድህነት ዓለም ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ለምን እንደዚህ ዐይነቱን ትልቅ የአውሮፕላን ጣቢያ ለመስራት አስፈለገ? እንደሚታወቀው የአገራችን ኢኮኖሚ በጣም የተዝረከረከና ስራ ለሚፈልገው ህዝባችን በቂ የስራ መስክ የመስጠት ኃይል የለውም። ሌላው ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት የውጭ ኢንቬስተሮችን ለማስተናገድ ሲባል ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር የማይጣጣሙ ትላልቅ ሆቴልቤቶች በመሰራት ለህዝቡ ሊዳረሱ የሚችሉ ምግብ ነክ ነገሮችና ቅባቶች፣ መብራትና ውሃን በመጋራት የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት አድርገዋል። እንደዚህ ዐይነት ትልቅ የአውሮፕላን ጣቢያ ሲሰራ የግዴታ ሁኔታውን የሚያባብስው እንጂ ችግሩን የሚፈታ አይደለም። አደጉ የሚባሉ አገሮችን የኢኮኖሚ ሁኔታ ስናጠና የውስጥ ገበያ ከማደጉና በአገር አቀፍ ደረጃ የተስተካከለ ግንባታ ከመካሄዱ በፊት እንደዚህ ዐይነት ትልቅ ፕሮጀክት ላይ በፍጹም አልተረባረቡም። ይህም ማለት የውስጡ ኢኮኖሚ ከመዳበሩ፣ ከተማዎች በስነስርዓት ከመገንባታቸው በፊት የውጭ ጎብኝዎችን ለማስደሰት ተብለው የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ነው የሚያመዝነው። በተጨማሪም እንደዚህ ዐይነት ትልቅ ፕሮጀክት ከመሰራቱ በፊት ሰፊ ጥናት ይካሄዳል። ጥቅሙና ጉዳቱ በደንብ ይጠናል። በአካባቢው ህዝብ ላይ ሰለሚደርሰው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ በደንብ ይገመገማል። በአካባቢና በጤንነት ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንደዚህ በደንብ ይጠናል። ለምሳሌ አውሮፕላኖች ሲነሱና ሲያርፉ፣ እንደዚሁም አካባቢውን ለቀው እስኪወጡ ድረስ ስለሚያደርሱት ጩኸትና በሰው ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ በደንብ ይመረመራል። ከህዝብም ዘንድ ተቃውሞ ካለ አይ ብዙ ነገሮች እንዲሻሻሉ፣ አሊያም ደግሞ ፕሮጀክቱ እንዳይሰራ ይደረጋል። ባጭሩ በሰው ላይ ዝም ተብሎ የሚጫን ነገር የለም። እንደምገምተው ከሆን በአገራችን ምድር የሚሰሩት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ዝም ተብለው በጉልበትና በአወሁኝ ባይነት የሚሰሩ ናቸው። ስለሆነም የከተማው አስተዳደርም ሆነ መንግስት ይህንን ጉዳይ ጠጋ ብለው ቢያጠኑት መልካም ነው።

ከዚህ ሰፋ ያለ ትንተና ስንነሳ የእነ ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህንና ለኧርንስት ያንግ ተቀጥሮና በአዲስ አበባ ተንደላንቆ የሚኖረው ዘመደነህ ነጋቱ የሚባለው የአሜሪካን ዜግነት ያለው፣ በትውልዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ግለሰብ ዋና ዓላማቸው የአገራችንን ሀብት ለውጭ ኩባንያዎች እንዲቸበቸቡ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው። የውጭ ከበርቴዎች በአበባ ተከላና በአንዳንድ ለውጭ ገበያ በሚሆኑ ሰብሎች እንዲሰማሩ ወደ ውጭ በማውጣት እዚያው እንዲፈበረክ ማድረግና፣ በሪል ስቴት ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የህዝባችንን ድህነት ጥልቀት መስጠትና፣ ህዝብን ከቀየው እንዲፈናቀል ማድረግ ነው። እንደነዚህ ዐይነት ስማርት የመሳሰሉ “የኢኮኖሚ አማካሪዎች” በመሰረቱ የዘመናዊነትና የነፃነት አስተሳሰብ የሌላቸው በመሆናቸው በተለይም በኢንዱስትሪና በንግድ ቻምበር ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩትንና ሌሎች የኢኮኖሚ ኤሊቶችን ያባልጋሉ። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲተክሉና የስራ መስክ እንዲፈጥሩ ምክር የሚሰጡ ሳይሆኑ፣ በንግድ አማካይነት የአገር ውስጥ ሀብት ወደ ውጭ የሚፈስበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ። እንደነዚህ የመሳሰሉት ብቻ ሳይሆኑ በፋይናንስና በኢኮኖሚ ሚኒስተር ውስጥም በዓለም ባንክ ደሞዝ እየተከፈላቸው በፖወር ፖይንት የተደገፉ ፉርሽ ገለጻ የሚሰጡና ሚኒስተሮችን የሚያማክሩት በሙሉ ዋና ዓላማቸው በአገራችን ምድር ጠንካራና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ነው። ሰፊው ህዝብ ለማኝና ደሃ ሆኖ እንዲቀር ነው ዋናው ተግባራቸው። በአገራችን ምድር እንደ ታይዋን፣ እንደ ደቡብ ኮሪያና ቻይና የመሳሰሉ ውስጠ-ኃይል ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች እንዳይታይ ነው  ጥረታቸው።  ምናልባት እንደዚህ ብለው አያስቡም ይሆናል። የሰለጠኑበት ከሳይንስና ከፍልስፍና፣ እንዲሁም ከሶስይሎጂና ከሰው ልጅ ህይወትና ፍላጎት ውጭ የሚሰጠው ትምህርት ጭንቅላታቸውን ስለቀረፀው የአንድ አገር ኢኮኖሚ በዚህ መልክ የሚዋቀር ሊመስላቸው ይችላል።

ይህ ዐይነቱ ችግር ከምንድነው የሚመነጨው? ለዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ዋናው ችግር የኢኮኖሚ ዕድገትንና ሌሎች የህብረተሰብ ጥያቄዎችን በሚመለከት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ስለማይሰጥና በምሁሮች መሀከል ምንም ዐይነት ክርክር ስለማይካሄድ ነው። በተለይም በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚለው ኤሊት ስለህበረተሰብና ስለኢኮኖሚ ዕድገት ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በአብዛኛዎቹ አስተሳሰብ በኢኮኖሚ ሳይንሰ ውስጥ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ብቻ ናቸው ያሉት።  ስለዚህም ከብዙ አገሮች ልምድ እንደሚታየው በአገራችን ምድር ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ በአብዛኛዎች አስተሳሰብ መንፈስ ውስጥ ተቀርጿል። በሌላ ወገን ግን በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት እንዴት ድህነትና ረሃብ እንደሚቀረፉ፣ መንደሮችና ከተማዎች  እንዴት እንደሚገነቡና ለሰፊው ህዝብ የስራ-መስክ ዕድል እንዴት ሊዘጋጅ እንደሚችልና፣ ለህዛብችን የሚኖርበት መጠለያ እንዴት እንደሚሰራ ሊነግሩን በፍጹም አይችሉም። ይሁንና የካፒታሊስት አገርቶችንም ሆነ በኋላ የአደጉ ኢኮኖሚዎችን፣ የጃፓንን በሚጂ ዲናስቲ ዘመን፣ ከ1917 ዓ. ም፣ በተለይም ደግሞ ከ1945 ዓ.ም በኋላ የሶቭየት ህብረትን፣ ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ  የቻይናን ጉዳይ፣ ከ1950ዎች ዓመታት ጀምሮ ደግሞ የደቡብ ኮርያን፣ የሲንጋፖርንና የታይዋንን የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገትና አገነባብ ታሪክ ስንመለከት ነገሩ በነፃ ገበያና በሶሻሊስት ኢኮኖሚ መሀከል አንዱን መምረጥ አለብን ብለው ችግር በመፍጠር ሳይሆን ዕድገትን ያመጡት በታቀደና በዕውቀት በመመራት ብቻ ነው። ወደ ውስጥ ኃይላቸውን ሰብሰብ በማድረግና በታታሪነት በመነሳት ነው። በሴራ ፖለቲካና በመጠላለፍ በመጠመድ አይደለም በቴክኖሎጂ መጥቀው መሄድ የቻሉት።  ምክንያቱም የሴራ ፖለቲካ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ስለማያመች ነው። በአሲያቶች መንፈስ ውስጥ ሴራ የሚባል ነገር ያለ አይመስለኝም። ልዩ ፍጡሮች ናቸው። እንደኛው መንፈሳቸው በጥርጣሬና በተንኮል የተተበተበ አይደለም።

ለውጥ መጣ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ያለውንም ሁኔታ ስንመለከት ያለው ችግር ፖለቲካዊ ሴራ የበዛበትና በምንም ዐይነትና ዕውቀት ያልተደገፈ ስለሆነ መሰራት የሚገባቻው ነገሮች በሙሉ እስካሁን ድረስ ሳይሰሩ ቀርተዋል። ያለውና የተወሳሰበውም ችግር ለብዙ ዓመታት በዚህ እንደሚቀጥል መገመቱ ከባድ አይሆንም። ምክንያቱም አዲስ የለውጥ ኃይል እየተባለ የሚሞገሰው አገዛዝ ከወያኔ አስተሳሰብና አሰራር በፍጹም ያልተላቀቀ በመሆኑ ነው። ስለዚህም ነው ከኢኮኖሚው ድቀት ባሻገር የፖለቲካው መስክም ውስጥ ትርምስ የሚታየው። ፓለቲካዊ ግልጽነት ከሌለ፣ የፓለቲካው ፍልስፍና ምን እንደሆን ካልታወቀ ደግሞ አንድን ማህበረሰብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ማድረግ በፍጹም አይቻልም። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                                      fekadubekele@gmx.de

ማሳሰቢያ፤ አንዳንዶች ይህን ጽሁፍ የሚያነቡ እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ መውጣቱ የጊዜው  አንገብጋቢ ጥያቄ አይደለም፤

               አንገብጋቢው ጉዳይ አሁን አገራችን ያለችበት የጦርነት ጊዜና፣ በህዝባችን ላይ የሚፈጸመው ለጭንቅላት

              የሚዘገንን ድርጊት  ነው ብለው ሊናገሩ ይችላሉ። እኔም በእዚህ አባብል እስማማለሁ። በሌላ ወገን ግን

             በህዝባችን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ሁለመንታዊ ነው። ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ የስነ-ልቦናና፣ የአካባቢ

             ውድመትና ሌሎችም ነገሮች፣ በአጭሩ አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ማዳከምና ሰፊውን ህዝብ አቅመ-ቢስ 

             ማድረግ ነው። ስለዚህ ሁሉም በቻለው መልክና ስራ-በመከፋፈል ያለውን  የተወሳሰበ ችግር በምሁራዊ መነፅር

             በመቃኘት መጻፍ ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ደግሞ  ከኢትዮጵያ ምድር ጦርነት እንዲወገድና ህዝባችንም እፎይ

             ብሎ እንዲኖር ከተፈለገ የግዴታ የመንግስትና የፖለቲካው መስክ መመርመር አለባቸው። በመንግስትና

             በፖለቲካው መስክ ላይ ብዙ ያልተገለጸለትና መንፈሱ በሳይንስና በሊበራሊዝም አስተሳሰብ ያልታነፀ ጥቂት

             የማይባል ኃይል ስላለ ጦርነቱ ሲቀጥል ብቻ ነው በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚችለው። ይህንን ሁሉ እሳቤ

             ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

 

 

                                  Abraham Maslow’s hierarchy of needs

 

 

 

 

ጠቃሚ የኢኮኖሚክስ መጽሀፎች፣

Adam Smith; An Inquiry into the Nature and Causes of the Wealth of Nations,

Pennsylvania State University Press, 2005

Arghiri Emanuel; Unequal Exchange: A Study of the Imperialism of Trade, New York, 1972

Fekadu Bekele; African Predicaments and the method of Solving them Effectively, Berlin 2016

Fekadu Bekele, ካፒታሊዝም፡ የካፒታሊዝም ዕድገትና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍልስፍና አፀናነስ በርሊን፣ 1994

Dambisa Moyo;  Dead Aid. Why aid is not working and how there is a better way for Africa,

New York, 2009

Ernest Feder; Strawberry Imperialism: Studies to the Agricultural Crisis of Latin American

Countries, Frankfurt am Main, 1980

Ernst Mandel; Marxist Economic Theory, 1&2, Frankfurt am Main, 1968

Karl Marx; Capital: Acritical Analysis of Capitalist Production, Vol. 1,2 & 3, New York, 1975

Paul Mattick; Marx and Keynes, Frankfurt am Main, 1969

Rod Hill &Tony Myatt; The Economics Anti-Textbook: A Critical Thinker`s Guide to

Micro-Economics, London/New York, 2010

Samir Amin; Accumulation on a World Scale: A Critique of the Theory of Underdevelopment,

New York/ London, 1974

Stephan Krüger; Keynes versus Marx?,  Hamburg, 1984

Steve Keen; Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned? New York, 2011

Tom Burgis; The Looting Machine: Warlords, Tycoons, Smugglers and

the systematic theft of Africa`s Wealth, London, 2015

Thomas Piketty; Capital in the Twenty-First Century, London, 2014

TomአSedláček; Good and Bad Economy, München, 2009

Ulrike Hermann; The Victory of Capitalism: How Wealth comes in the World:

The History of Growth, Money and Crisis, München/Berlin, 2016

Vernard Foley; The Social Physics of Adam Smith, Indiana, 1976

Vivian Walsh & Harvey Gram; Classical and Neoclassical Theories of General Equilibrium:

Historical Origins and Mathematical Structure, New York, 1980