[gtranslate]

የኦሮሙማ ፖለቲካ ብሎ ነገር የለም! ኦሮሙማ መነገጃና የራስን

ፍላጎት ወይም ኢጎ ማሟያ መሳሪያ ነው!

                                                                       ፈቃዱ በቀለ (/)

                                                                                     ግንቦት 12 2023

ከፖለቲካ ቲዎሪና ትንተና አንፃር ሲታይ ኦሮሙማ የሚለው አባባል ትርጉም የሌለው ነው። ኦሮሙማ የሚለው አባባል የኦሮሞን የበላይነት እናሰፍናለን የሚባል ከሆነም ትክክል አይደለም። በጠቅላላው እንደ ኦሮሞ የሚቆጠረው ብሄረሰብ በጋርዮሽ የበላይነቱን ሊያስፍንና በማንኛውም ረገድ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተጠቃሚ ሊሆን በፍጹም አይችልም፤ በዚህም አማካይነት በጥቅል የበላይነቱን ሊጎናጸፍ አይችልም። በታሪክ ውስጥም ታይቶ አይታወቅም። ኦሮሙማ የሚባለው አነጋገር በመሰረቱ በዝቅተኛ ስሜት የተዋጡትን የእነ አቢይንና የእነ ሺመልስ አብዲሳን የስልጣን ጥም ማርኪያ መሳሪያ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ኦሮሞዎች ነን የሚሉትም ሆነ ሌሎች ብሄረሰቦች ንጹህ በንጹህ ከሌሎች ጋር ሳይጋቡና ሳይቀላቀሉ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ አይደሉም። ለምሳሌ አቢይ አህመድ በእናቱ መርሃቤቴ ሲሆን፣ በአባቱ ደግሞ ደግሞ ኤርትራዊ ወይም ሌላ የውጭ አገር ዜጋ እንደሆነ ይነገራል። በብዛት የኦሮሞ ቋንቋ በሚነገርበት ቦታ ስለተወለደና ስላደገ፣ እንዲሁም ሶሽላይዝድ ስለሆነ በኦሮሞ ስም ይነግዳል። ጀዋር መሀመድም እንደዚሁ በአባቱ የመናዊ፣ በእናቱ ደግሞ መንዜ ነው። አብዛኛው ኦሮሞ ነኝ የሚለው ኤሊት፣ በተለይም እነ ሌንጮ ባቲ በአባቶቻቸው የጎንደሬ ቄሶች ናቸው። ስለዚህም ኦሩሙማ የሚለው ስም ተጎሳቁሎ ለሚኖረውና፣ ከሌሎቹ እህቶቹና ወንድሞቹ ኢትዮጵውያን ጋር በመሆን ዕውነተኛ ነፃነትንና ዲሞክራሲን የሚመኘውን ሰፊውን የኦሮሞ ተወላጅ የሆነውን ምንም አይጠቅመውም። እንዲያውም የድህነቱን ዘመን የሚያራዝምበትና ግራ ተጋብቶ እንዲኖር የሚያደርገው የጥቂት ኤሊቶች መጠቀሚያ መሳሪያ ነው።

ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ፣ አንድ የገዢ መደብ ከየትኛውም ብሄረሰብ ይምጣ የብሄረሰቤን ጥቅም አስጠብቃለሁ፣ የበላይነቱንም አሰፍናለሁ የሚል ከሆነ የግዴታ የሚመራበት የራሱ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍናና የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲኖረው ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በሚኖርበት አገር ውስጥ ደግሞ ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ የሚሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊነደፍ አይቻልም፤ ወይም ደግሞ ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ የሚሆን ወይም ሊያገለግል የሚችል ህገ-መንግስት ማውጣት አይቻልም። በጋዳ ህግ ነው ለመተዳደር የምንፈልገው የሚባል ከሆነ ደግሞ ወደ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋው፣ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣው ህዝባችን ዕጣስ ምን ሊሆን ነው? ሁሉም በመገደድ ኋላ-ቀር የሆነውን የወራሪዎችን የጋዳ ስርዓት የሚባለውን መቀበል አለበት ወይ? ወደ ኋላ እንጓዝ ካልተባለ በስተቀር፣ ይህ ዐይነቱ አካሄድ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ዕድል በሚወስኑበት ዓለም ውስጥ ሊሰራ በፍጹም አይችልም። እንደሚታወቀው የኦሮሞ ኤሊቶች እንደሚነግሩን ወይም ሊያሳምኑን እንደሚፈልጉት የጋዳ ስርዓት በፍጹም ዲሞክራሲያዊ አልነበረም። በተለይም ሴቶችን ክግል ሀብት ያገለለና የጥቂት ወንዶች መሳሪያ የነበረ ነው። ስለሆነም ከፖለቲካ ሳይንስ ወይም ቲዎሪ አንፃር ኦሮሙማ የሚለው አባባል ማወናበጃ መሳሪያ ብቻ ነው።

ከዚህ ወጣ ብለን ስንሄድ በሚገባ መታየት ያለበት ጉዳይ አብዛኛውን ሬሶርስ እየተቆጣጠሩና ጦርነት በየቦታው እየከፈቱ ለኦሮሞ ብሄረሰብ ብቻ የሚስማማና ከድህነት የሚያላቅቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ በፍጹም አይቻልም። ከኢኮኖሚክስ ቲዎሪና ፖሊሲም አንፃር ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ የሚስማማ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ በፍጹም አይቻልም። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ነው። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በምርት ማምረቻ ቦታዎችም ሆነ በንግድ እንቅስቃሴ በመሳተፍ፣ ወይም በገበያ ውስጥ ስለሚገናኝ፣ ከሶስይሎጂ ቲዎሪ አንፃር ይህ ዐይነቱ በምርትም ሆነ በገበያ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ሁሉንም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ የሚመለከት ነው። ስለሆነም ለኦሮሞ ብሄረሰብ የሚሆንና የሚስማማ ፋብሪካ መክፈትና፣ ምርትም ማምረት አይቻልም። ይህ ከሆነ ደግሞ የአፓርታይድ ስርዓት መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በዐይነትም ሆነ በብዛት እንዳያድግ ማገድ ይሆናል። በአንድ አገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ፈጠራ ሊታዩ የሚችሉት የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲሳተፉ ብቻ ነው። በኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥም ሁለ-ገብ የሆነ ዕድገት ሊመጣና አዳዲስ የማምረቻ መሳሪያዎችና ምርቶችም ሊፈጠሩና ሊመረቱ የሚችሉት ከተለያየ ብሄረሰብ የተወለዱ ግለሰቦች ሲሳተፉበትና፣ ችሎታቸውን ወይም ዕውቀታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎች ሲፈጠሩላቸው ብቻ ነው። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ ከአንድ ብሄረሰብ በተውጣጣ ኃይል ብቻ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት አይቻልም፤ በታሪክም ውስጥ በሌሎች አገሮችም አልታየም። ከዚህ ስንነሳ የኦሮሞ ብሄረሰብም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለኑሮው ማስተማመኛ የሚሆነው ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት ያስፈልገዋል። በሌላ ወገን ግን እንደምንከታተለው ከሆነ አብዛኛውን የጥሬ-ሀብት የሚቆጣጠሩት ጥቂት የኦሮሞ ባለሀብታሞችና፣ ከዚኸኛውና ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ጥቂት የኦሮሞ ኤሊቶችም ደግሞ ጥሬ-ሀብትን ለመቆጣጠር ሲሉ ሌሎች ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ለመቆጣጠር ወረራ በማካሄድ፣ አንዳንድ የነቁና አልታዘዝም የሚሏቸውን የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆችን በጠራራ ፀሀይ እንደሚገድሏቸው ነው። ስለሆነም የኦሮሞ ኤሊት ሬሶርሶችናን፣ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ የከተማ ቦታዎችን በመቆጣጠርና ቤት በመስራት የበላይነቱን ለማረጋገጥ እየተሽቀዳደመ ይገኛል። ይህም የሚያመለክተው ጥቂቱን የኦሮሞ ኤሊት የሚጠቅም የኢኮኖሚ መሰረት እየተዘረጋ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የኦሮሞ የኢኮኖሚ ፖሊሲም የሚባል ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም። እንደምናየውና እንደምንከታተለው ከሆነ አሁንም ቢሆን እነ አቢይ አህመድ ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሰፋ ያለ የስራ-መስክ በመክፈትና የአገር ውስጥ ገበያ በመገንባት ሰፊውን ህዝብ ከድህነት የሚያላቅቀው ፖሊሲ ሳይሆን የሚከተሉት፣ ይባስ ብሎ ሰፊውን ህዝብ ወደድህነት የሚገፈትረው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ነው። በተለይም የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በየጊዜው ዝቅ እንዲል ማድረግ የሚያረጋግጠው የኦሮሙማ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግንና ሳይንስን እንደማይረዱ ነው። በተደጋጋሚ በሚደረገው የገንዘብ ቅነሳ ምክንያት የተነሳ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚነግረን አብዛኛው ህዝብ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፤ ምክንያቱም ገንዘቡ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በየጊዜው የሚቀንስ ከሆነ የገንዘቡ የመግዛት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ስለሚቀንስ ነው። ይህ ዐይነቱ ተከታታይነት ያለው የገንዘብ ቅነሳ፣ በተለይም ሬሶርሶችን ከሚጋሩት ካለቅጥና ካለ አላስፈላጊነት ከሚሰሩት ሆቴልቤቶች ጋር ሲደመር ለዋጋ ግሽበት ዋናው ምክንያት ሆኗል። በተለይም ደግሞ ጦርነት በሚካሄድበት በአማራው ክልል የምርትና የንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱም የተነሳ የአዲስ አበባ ኗሪ ህዝብ በኑሮ ውድነት እንደሚሰቃይ ይነገራል። ጦርነት በሰፊው ህዝብ ላይ አውጆ ጤናማና ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅም ሰፋ ያለና መሰረቱ ጠንካራ የሆነ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አይቻልም።

ከዚህ አጭር ትንተና ስንነሳ  የኦሮሙማን አገዛዝ የሶሻል መሰረትና ከውጭው ዓለም ጋር ያለውን ግኑኝነት በሚገባ መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ተቀበላችሁም  አልተቀበላችሁም ከፖለቲካ ሳይንስ አንፃር የዛሬው በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ አውቶኖመስ ወይም ነፃ በሆነ መልክ በራሱ ሃሳብና  ፍልስፍና የሚንቀሳቀስ አይደለም። ከፖለቲካ ሳይንስ አንፃር በኦሮሞ ብሄረሰብ ስም የሚነግድ ፋሺሽታዊ አገዛዝ የሚመስል የንዑስ ከበርቴው መደብ ነው  የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠረው። የሶሻል መሰረቱን (Social Base) ስንመረምር ደግሞ ለጥቅሙ የተገዛ የዛሬን ብቻ የሚያስብና ዛሬ ብቻ የሚኖር የሚመስለውና ለመጭው ትውልድ የማያስብ ሰፋ ያለ የደነቆረ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣ የንዑስ ከበርቴ መደብ ነው። ይህ ዐይነቱ የአገዛዙ የሶሻል መሰረት በአዲስ የፍጆታ አጠቃቀም በማበድ ከፍተኛ የሆነ የባህል ውድቀትን እያስከተለና፣ በተለይም ደግሞ ለታዳጊው ትውልድ መጥፎ ምሳሌ እየሆነ ነው። ይህ ዐይነቱ አገዛዝና የሶሻል መሰረቱ በዓለም አቀፍ አገዛዝ የፀረ-ዕድገት፣ የፀረ-ሰላም፣ የፀረ-ሳይንስና የጦርነት ሂራርኪ ውስጥ በመካተትና በህዛባችን ላይ ጦርነት በመክፍት ጠቅላላውን ህዝብ፣ ተራውን የኦሮሞም ብሄረሰብ ጭምር ሰላም እየነሳው ነው። ስለሆነም የአቢይ አህመድና የሺመልስ አብዲሳ አገዛዝ በውጭ ኃይል የሚጠመዘዝና የራሱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍላጎት፣ እንዲሁም ሶሻል ስታተስ የሚያሟላና፣ ይህንንም ላለማጣት የሚፍጨረጨር  ነው። ከውጭው ኃይል ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ከመስራቱ የተነሳ የፀጥታውን መዋቅርና ፖሊሱን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ህዝባችንን ሰላም ነስቶታል። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነቱን ገፎበታል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ተዝናንቶ መንቀሳቀስ፣ ማምረትና መፍጠር በፍጹም አይችልም።

ሰለሆነም የኦሮሙማ አገዛዝ እየተባለ የሚጠራው በአቢይ አህመድ የሚገዛው አመራር የአገራችንንን ዕድገት ወደ ኋላ እየጎተተው ነው። የተሟላ ሰላም ባልሰፈነበት አገር ውስጥ የፈጠራ ስራ ማካሄድ በፍጹም አይቻልም።  ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረዢም ጊዜ አንፃር ኢኮኖሚያዊ ዕቅድ በፍጹም ማውጣት አይቻልም። በመዋዕለ-ነዋይ ለመሳተፍ የሚፈልግ ግለሰብ ሀብታም ከፖለቲካ አንፃር ሲታይ እርግጠኝነት እንዲሰማው ያስፈልጋል። በፈለገው ቦታ ሄዶ ሀብቱን በስራ ላይ ለማዋል የፖለቲካው አየር እንዲስማማው ያስፈልገዋል። ሀብቱም የማይዘረፍ፣ ወይንም ደግሞ ካለአግባብ ቀረጥ እንዲከፍል የማይገደድ መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ሌላ ቦታ ሄዶ ሀብቱን በመዋዕለ-ነዋይ መልክ ተግባራዊ የሚያደርግ ግለሰብ ሀብታም በአካባቢው አስፈላጊውን የጥሬ-ሀብት፣ የሰለጠነ ሰራተኛ ወይም የሰው ኃይልና፣ ከዚያም በላይ ያመረተውን ምርት የሚገዛ የሰው ኃይል(Buying power) ያስፈልገዋል። ስለገበያ ኢኮኖሚ የምናወራ ከሆነ ደግሞ የገበያ ኢኮኖሚ ብዙ ነገሮች ሲሟሉ ነው ቀስ በቀስ እያለ ዕምርታን የሚያገኘው። በሁሉም አቅጣጫ በማደግ ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው ቦታና ጊዜ(Space and Time) ብለን የምንጠራቸው መሰረታዊ ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው። ቦታ ወይም space ሲባል በደንብ የተደራጀ ከተማ፣ የተለያዩ ዕቃዎችና ምግቦች የሚሸጡባቸው የገበያ አዳራሾች፣ የመገበያያ ቦታዎችና፣ የመኖሪያ ቤቶችና ልዩ ልዩ የአገልግሎት መሸጫ ተቋማትና መደብሮች፣ ሆስፒታሎችና ትምህርትቤቶች፣ እንዲሁም የሙያ ማስልጠኛ ማዕከሎችና ሌሎች የስፖርት እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባቸው ቦታዎች ማለቴ ነው።  ይህ ሲሆን ብቻ ግልጽነት ያለው የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል። ስለጊዜ ሲወራ ደግሞ፣ ጊዜ ራሱ የኢኮኖሚ ፋክተር እንደመሆኑ መጠን የሚመረቱት ምርቶች ሳይበላሹ  በሚያስፈልግበት ጊዜ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀሱና ለሺያጩና ለገዢው የሚደርሱ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የተቀላጠፈ የተለያየ የትራንስፖርቴሽንና የማመላለሻ  ሁኔታና መንገድ መፈጠር አለባቸው። ሁሉም ነገር በተቀላጠፈና በንጽህና መካሄድ አለባቸው።

ነገሩን ለማሳጠር፣ የኦሮሙማ ፖለቲካ ፍልስፍና የሌለው የንዑስ ከበርቴው ወይም ኤሊት ነኝ የሚለው ማደናገሪያ ዘዴ ነው። እወክለዋለሁ የሚለውን ብሄረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ጥቅም በፍጹም ሊያሟላ የሚችል አይደለም። የመብት ጥያቄ ደግሞ ለአንድ ብሄረሰብ ተቆርሶ ወይም ተለክቶ የሚሰጥ አይደለም። ፖለቲካ ከነፃነት፣ ወይም ዕውነተኛ ሊበሪቲ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ የእያንዳንዱን ግለሰብ ነፃነት ጉዳይ የሚመለከት ነው፤ በሌላ አነጋገር የብሄረሰብ ፖለቲካ የሚባልና፣ ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ የሚያገለግል የፖለቲካ ነፃነት የለም። ከዚህ ዐይነቱ ማደናበሪያና ወደ ኋላ የሚጎትት የኦሮሙማ ፖለቲካ ከሚሉት ለመላቀቅ የግዴታ በብሄረሰብ ስም ከሚነግድ የፖለቲካ ኤሊት ፖለቲካው በመላቀቅ የህግ የበላይነት ተግባራዊ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ስለህግ የበላይነት ስናወራ ደግሞ ሶሶቱም የመንግስት አካላት በህግ የበላይነት የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ኤክስኪዩቲቩን ወይም የስራ አስፈጻሚውን ደግሞ ፓርሊያሜንቱ ወይም የህዝብ ተወካዮች መቆጣጠር አለባቸው። ወታደሩም ሆነ የፖሊስና የፀጥታው ኃይል በአንድ ግለሰብ ቁጥጥር ስር መውደቅ የለባቸውም። ወታደሩንም ሊያዝ የሚችለው ወይም ጦርነት የሚያውጀው አንድ ግለሰብ ብቻውን ሳይሆን፣ በፖርሊያሜንት ውስጥ በቂ ክርክር ከተካሄደበት በኋላ ነው። ይህም ማለት የህዝብ ተወካዮች በህዝብ የተመረጡ እንደመሆናቸው መጠን ከውጭ የሚመጣውን፣ ወይም ከውስጥ ሆኖ ሰላም የሚነሳውን ኃይል በምን ዐይነት ዘዴ ለመቆጣጠር ይቻል እንደሆነ በሰፊው ማጥናትና መከራከር አለባቸው። ከአቅማቸው በላይ ከሆነ ደግሞ በአገር ውስጥ በተለያየ ሙያ የተደራጁና የሰለጠኑ፣ ሙያቸው መንግስትን ማማከር የሆነ ድርጅቶችን መቅጠርና ምክር እንዲሰጧቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ እነ አቢይ አህመድና ጠቅላላው በኦሮሞ ብሄረሰብ ስም የሚነግደው ኤሊት እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ፖለቲካ በመከተል ጠቅላላውን ህዝባችንን አደንቁሮ እያስቀረው ነው። የዕድገቱን ወይም የስልጣኔውን በር ሁሉ ዘግቶበታል። ስለሆነም የአገራችንን ፖለቲካ ከዕውነተኛ የፖለቲካ ሳይንስ አንፃር ነው መመርመር ያለብን እንጂ ኦሮሙማ እያልን ህዝቡን ግራ ባናጋባው ይሻላል። የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ሁሉም በሚገባው መልክ ማስቀመጥ ወይም ማተት ያስፈልጋል። ስልጣንን የጨበጠው በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ የኦሮሙንም ሆነ የጠቅላላውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማይወክልና ፍላጎቱንም እንደማያስጠብቅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ከሁለት ቀን በፊት ባሰራጨሁት ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአቢይ አህመድ አገዛዝ በውጭ ኃይል፣ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመታዘዝና በመጠምዘዝ፣ በተለይም በአማራው ብሄረሰብ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ በጠቅላላው ህዝባችን ላይ ጦርነት በመክፈት ሰላም የነሳ ነው። በመሆኑም በአገራችን ምድር ዘላቂ ሰላም እንዲስፈን ከተፈለገ ይህንን ፈሺሽታዊ አገዛዝና ክወጭ ሆኖ የሚጠመዝዘውን ኃይል ከህዝባችን ጫንቃ ላይ ማንሳት ያስፈልጋል። የተሟላ ሰላምና ነፃነት በሌለበት አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነና፣ በተለይም ደግሞ ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ወይም ደግሞ ከድህነት የሚያላቅቀው ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት ስለማይቻል መሰረታዊው ጥያቄና ትግላችን እንደዚህ ዐይነቱን የስልጣኔ ጠንቅ የሆነና የተደናቆረ ፖለቲካን የሚያካሄድ ኃይልና አጋሮቹን አሽቀንጥሮ መጣል ነው። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de           

www.fekadubekele.com

 

ማሳሰቢያ፤ በአንዳንድ ግለሰቦችና የሚዲያ ሰዎች የሚናፈሰው ወሬ ኃይላችንን ስናጠናክር አሜሪካ

             ከጎናችን ይቆማል፣ ይደግፈናልም የሚለው አባባል እጅግ አደገኛና ትጥቅ አስፈቺ ነው።

             አሜሪካ የጠነከረን ኃይል ሳይሆን የሚፈልገው ተገዢውና ተላላኪው፣ እንዲሁም

             ከውስጥ ህዝቡን የሚያዳክምለትን ኃይል ብቻ ነው። ስለሆነም ነው ወያኔን ይደግፈውና

             ያስታጥቀው የነበረው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአንድ አገር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ

             ስርዓት እንዲሰፍንና የሰፊውን ህዝብ የነቃ ተሳትፎ የሚሻ አይደለም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ

             ላይ የተመሰረተም የኢኮኖሚ ግንባታ አጋዥ ኃይል አይደለም።

             ሌላው አንድ ግለሰብ ኢምፔሪያሊዝም ብሎ ሲጽፍ ካለምክንያት አይደለም። ጽንሰ-ሃሳቡ

             ከሁለ ሺህ ዓመት በፊት የነበረና፣ ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ደግሞ ካፒታሊዝም

             በከፍተኛ ደረጃ  እያደገ ሲመጣ የጥሬ-ሀብትን ለመቀራመትና የሌሎች አገሮችን ዕድገት

             እየተቀናቀና ሲመጣ የተሰጠው የወራሪነት መጠሪያው ስም ነው። ስለሆነም ጽንሰ-ሃሳቡ

             የፖለቲካ ሳይንስ ስም ስለሆነ አሜሪካን በዚህ መልክ ሰለተጠራ ግራ መጋባት አያስፈልግም።