[gtranslate]

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

                                                                                      ፈቃዱ በቀለ(/)

                                                                                                                                                                                                        ሰኔ 2 2016 (ሰኔ 10 2024)

 

በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር በመዋደጀታቸው ምክንያት ነው የሚል በሳይንስና በኢምፔሪካል ያልተረጋገጠ በእንግሊዘኛ የተጻፈ ጽሁፍ አስነብቦናል። በሌላ ወገን ደግሞ በቬትናምና በቻይና መሀከል ያለውን ለኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት የሆነውን ልዩነት ለማብራራት በፍጹም አልቻለም። የቻይናው በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በምርምር ላይ የተመሰረተ ሲሆን የቬትናሙ የኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ ሰፋ ባለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ስለሆነም በሁለቱ አገሮች መሀከል የሰማይና የመሬትን ልዩነት አለ ማለት ይቻላል።

ዋናው መሰረተ-ሃሳብ ግን በሁለቱ አገሮች መሀከል ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ልዩነትና መሰረቱን ለማሳየት ሳይሆን ዮናስ ብሩ እንደሚለን በእርግጥስ ሁለቱ አገሮች ከአሜሪካን ጋር በመወዳጀታቸውና ከዚያ ቴክኖሎጂ በማግኘታቸው ነው ወይ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት  ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት? ወይስ ዋናው ምክንያት ዮናስ ብሩ እንደሚለን ሳይሆን ሌላ ነው? የሚለውን ጠጋ ብሎ ለመመርመር ነው። በመጀመሪያ ግን መሰረተ-ሃሳቡን ጠጋ ብሎ ለመረመረ በካፒታሊዝም ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲኖር፣ በሌላ ወገን ደግሞ ኋላ ላይ የተነሱ አገሮች፣ ለምሳሌ ጃፓን በ1868 ዓ.ም ጀምሮ፣ ራሺያ ደግሞ ቀደም ብሎ ማለትም በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የጥገና ለውጥ በማድረግና ቴክኖሎጂዎችን ከምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም በመኮረጅ ለስር ነቀል ለውጥ መሰረት ጥለዋል ማለት ችለዋል። ታላቁ ፔተር(Peter The Great) የአስተዳደር የጥገና ለውጥ በማድረግና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንዲተከሉ በማድረግ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ሰፋ ላለ የኢኮኖሚና የማህበራዊና የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ሊጥሉ ችለዋል።

ጃፓንም እንደዚሁ በሚጄ ዲናስቲ ቆራጥና የአገር ወዳድነት ስሜት በመነሳት በጊዜው የእንግሊዝና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ካደረጉባት ከበባና የማዳከም ስትራቴጂ ለመላቀቅ የምዕራቡን ቴክኖሎጂ በመኮረጅ ወይም በመቅዳትና ይህንን መሰረት በማድረግ የእነሱን ቴክኖሎጂ” መሰረት አድርጎ እነሱን መልሶ መዋጋት ያስፈልጋል” በሚል በወሰደችው በሳይንስና በቴክሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ችላለች። የጃፓን  መንግስት ይህንን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ተለያዩ የካፒታሊስት አገሮች ወጣቶችን ከላከና ሰልጠነው ከመጡ በኋላ በየቦታው ባቋቋመው ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመቹ የእንጂነሪንግ ትምህርትቤቶች ውስጥ ምርምርና ፈጠራ እንዲያደርጉ አመቺ ሁኔታ ፈጠረ። የሜጂ ዲናስቲ የተለያዩ አገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገት ካጠና በኋላ የተከተለው የዕድገት ስትራቴጂ በጊዜው የጀርመን አገዛዝ ይመረኮዝበት የነበረውን በተለይም የፍልስፍና፣ የሶስዮሎጂና የኢኮኖሚ ምሁራን ያዳበሩትን የኢኮኖሚ ቲዎሪ መመሪያ በማድረግ ነው። ይህም የኢኮኖሚ ቲዎሪ የታሪክ የኢኮኖሚ ትምህርት (Historical School) በመባል ሲታወቅ በአዳም ስሚዝና በዴቢድ ሬካርዶ የፈለቀውን የነፃ ንግድ ፖሊሲ የሚቃወም ነው። በእነ አዳም ስሚዝ ዕምነት የተለያየ ሬሶርስ ያላቸው አገሮች በዚያው ባላቸው ሪሶርስ ቢሰለጥኑና የንግድ ልውውጥ ቢያደርጉ በዚህም የተነሳ የኢኮኖሚ ዕድገትና የባህል ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ነው። በጊዜው እንደምሳሌ የተወሰደው እንግሊዝ በቴክኖሎጂ ቀድማ የሄደች አገርና በዚህም ላይ የተሻለ ግንዛቤ ስለነበራት በዚሁ ላይ ከሰለጠነችና ለምሳሌ በወይን ተከላና ጠመቃ ላይ የምታፈሰውን ሀብት ከቆጠበች ወይም ይህንን ለፖርቱጋል ከተወች ፖርቱጋል የኢንዱስትሪ የፍጆታ ምርቶችን ለምሳሌ እንደ ጨርቃ ጨርቅ የመሳሰሉትን ከእንግሊዝ ካስመጣችና በወይን ተከላና ጠመቃ ላይ ብቻ ካተኮረች ሁለቱም አገሮች የማምረቻ ዋጋን ይቀንሳሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሁለቱም አገሮች ተጠቃሚ(Comparative Cost Advantage) ይሆናሉ ይላሉ። ስለሆነም በጊዜው ፖርቱጋል የኢንዱስትሪ ምርቷን በመተው፣ በተለይም የጨርቃ ጨርቅ ማምረትን በመተዋና በወይን ተከላ ላይ ብቻ በመሰመራቷ በዓለም ገበያ ላይ የወይን ምርት ውጤት በሰፊው ሲዘረገፍ እንደተባለው ፖርቱጋል በቂ ገዢ ለማግኘት አልቻለችም። አብዛኛው የፖርቱጋል ገበሬም በጊዜው በወይን ተከላ ላይ ብቻ ስለተሰማራና ሌሎች ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎችን እርግፍ አድርጎ በመተዉ ፖርቱጋል ውስጥ ከፍተኛ ረሃብ ሊከሰት ቻለ። አዳም ስሚዝና ዴቪድ ሬካድርዶ ለማሳመን እንደሞከሩት በዚህ ዐይነቱ የንግድ ልውውጥ ተጠቃሚ ለመሆን የቻለችውና የኢኮኖሚ ዕድገትም ለማምጣት የቻለችው ፖርቱጋል ሳትሆን እንግሊዝ ብቻ ነበረች።

ይህንን የነፃ ንግድ ቲዎሪና ተግባርነቱንም በሚገባ የተከታተሉና ያጠኑ እንደ ፍሪድሪሽ ሊስት የመሳሰሉ የጀርመን ኢኮኖሚስቶች የእነ አዳም ስሚዝን የነፃ ንግድ ቲዎሪ በመቃወም አንድ አገር የነፃ የንግድ ልውውጥ ውስጥ ከመሰመራቷ በፊት የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ መገንባት አለባት። ከተማዎችና መንደሮችም በስነ-ስረዓት መገንባት አለባቸው።  የገበያ ኢኮኖሚ ሊዳብርና ግልጽነትም ሊኖረው የሚችለው ከተማዎች በዕቅድ ሲሰሩ ብቻ ነው። ለአገር ውስጥ የገበያ ዕድገት የግዴታ የመመላለሻ መንገዶች በተለይም የባቡር ሃዲድ መዘርጋት አለበት። ዕቃዎችን፣ በተጨማሪም የእርሻ ውጤቶችን ለማመላለስና ለገበያም ለማቅረብ የግዴታ የሰዎችና የዕቃዎች ማመላለሻ የባቡር ሃዲዶች መዘርጋት አለባቸው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በየቦታው የሙያ ማስልጠኛ ትምህርትቤቶችን በማስፋፋት ቴክኖሎጂዎችን ማዳበር ያስፈልጋል። በእነ ፍሪድሪሽ ሊስት ዕምነት፣ ትክክልም ነው አንድ ህዝብ በባህል ሊያድግና በረቀቀም መልክ ማሰብ የሚችለው በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ ሲኖረውና፣ የሚያማምሩ ከመተማዎችንና መንደሮችን ሲገነባ ነው። በዚህ ላይ የሚመሰረት ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ ብሄራዊ ስሜትን ያዳብራል። በሌላ አገርም በቀላሉ ሊጠቃ አይችልም ይላሉ የመርከንታሊስት ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ያላቸው ምሁራን። በመርከንታሊስት ኢኮኖሚ ምሁራን ዕምነት፣ ትክክልም ነው አንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ብቻ የሚካሄድበት ሆኖ መታየት የለበትም። የሰውም አስተሳሰብ ንጹህ በንጹህ ወደ ፍጆታ አጠቃቀም ብቻ መቀነስ የለበትም። የሰው ልጅ ማህበራዊ ስለሆነ(Social  Being) ስለሆነ የግዴታ ንቃተ-ህሊናውም መዳበር አለበት። ለንቃተ-ህሊና መዳበርና ራሱንም እንዲያውቅ የግዴታ ባህላዊ ክንዋኔ፣ ለምሳሌ እንደ ቲያትር፣ እንደኮሜዲ፣ እንደ ስፖርት መስሪያ ተቋማት፣ እንደ ሙዚየምና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች በሙሉ በከተማዎችም ሆነ በመንደሮች ውስጥ መስፋፋት አለባቸው። በዚህ መልክ ተሟልቶ የሚገነባ አገር ሰፊውን ህዝብ ያስተሳስራል። ስለሆነም የመርከንታሊስት ኢኮኖሚስቶች ከእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ነፃ ንግድ በብዙ ነገሮች ይለያሉ።  በመርከንታሊስት ኢኮኖሚስትች ዕምነት የኢኮኖሚ ዋናው ዓላማ የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት በማሟላት ጠንካራ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ወደ መገንባት የሚያመራ መሆን አለበት። በጠንካራ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ብቻ ነው አንድ አገር ወደ ውስጥ የምትጠነክረውና ወደ ውጭም ተደማጭነት ሊኖራት የሚችለው።

ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ዕድግትም ሰፋ ባለመልክ ለመተግበርና ውጤታማ ለመሆን እንደፍሪድሪሽ ሊስት በተለይም በውጭው ንግድ ላይ እንዲወሰድ የመከሩት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከውጭ የሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭመራ ማድረግና፣ ካስፈለገም የሚመጣውን መጠን መቀነስ ያስፈልጋል የሚል ነው። የጀርመን መንግስትም ይህንን ዐይነቱን የእነ ፍሪድሪሽ ሊስትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክር በመከተሉና በመተግበሩ የተነሳ ነው ጀርመን አንድ ትውልድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝንና ፈረንሳይን ቀድማ ለመሄድ  የቻለችው። በተለይም ቪሊሄም ሁምቦልድት በሚባለው ታላቅ ፈላስፋና ሳይንቲስት አማካይነት ተግባራዊ የሆነው አጠቃላይ የትምህርት የጥገና ለውጥ በጀርመን ምድር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሳይንቲስቶችን፣ የሂሳብ ተመራማሪዎችንና ኢንጂነሮችን እንደ አሸን እንዲፈልቁ አስቻለ። የሜጂ ዲናስቲና ተከታታዮች አገዛዞች ይህንን የጀርመኑን የኢኮኖሚ ዕድገት መንገድ በመከተል ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመገንባት የቻሉት።  ባጭሩ በሁለቱም አገሮች ውስጥና፤ በኋላ ላይ ደግሞ አሜሪካንም ጭምር የተወሰነ የኢኮኖሚ ናሺናሊዝም ስሜት ባይዳብርና አገዛዞችም ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባይከተሉ ኖሮ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ባልቻሉ ነበር። በጊዜው በአብርሃም ሊንከንና በእነ ሃሚልተን የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ቲዎሪ እርግፍ አድርጎ በመተውና ልዩ የሆነ የክሬዲት ሲስተም በማስፋፋትና ለማኑፋክቸሪንግ መስፋፋት የሚሆን ርካሽ ብድር ባይሰጥ ኖር አሜሪካ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት መገንባት ባልቻለች ነበር።

ይህ መሰረታዊ ሃሳብ እንዳለ ሆኖ  ሰፋ ላለ የካፒታሊዝም ዕድገትና የሀብት ክምችት በእንግሊዝ፣ በጀርመንና በአሜሪካን ምድር በከፍተኛ ደረጃ የሰራተኛው መደብ ይበዘበዝ ነበር። በተለይም በካፒታሊዝምና በእንዱስትሪ አብዮት የአፍላ ወቅት የወዝ አደሩ መደብ የሙያ ማህበር ስላልነበረውና መብቱንም ለማስጠበቅ ስለማይችል በቀን ከአስራሁለት ሰዓት በላይ መስራት የተለመደ ነበር።  የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በተስፋፋበት እንደ አሜሪካ በመሰለው አገር ደግሞ በተለይም ጥቁሩ በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝና በስራውም ቦታ ላይ የሚሰቃይ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው የኋላ ኋላ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድግትና የሀብት ክምችት ሊዳብር የቻለውም። ከብዙ አስርት ወይም መቶ ዓመት የኢኮኖሚ ክንዋኔና ዕድገት በኋላ ነው ቀስ በቀስ የወዝ አደሩ የመግዛት( Buying Power) ኃይል ሊጨምር የቻለውና ያመረተውን ምርት ከሞላ ጎደል እየገዛ መጠቀም የጀመረው። በተለይም የረጅም ጊዜ ዕድሜ ያላቸውን፣ እንደ መኪና፣ ማቀዝቀዣና ሌሎችም ምርቶችን የሰራተኛው መደብ እየገዛ መጠቀም የጀመረው ልዩ ዐይነት የብድር ሲይስተም መስፋፋት ከጀመረ በኋላ ነው። ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናውራበት ጊዜ በተለይም አንድ ህዝብ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። ለምሳሌ በዛሬው ወቅት አብዛኛዎቻችን የምንጠቅምባቸው ቴክኖሎጂዎች፣ የአኗኗር ስልቶችና አመጋገቦች ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የሚታወቁና የተለመዱም አልነበሩም። ይህም ማለት ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመታት፣ ወይም ከዚያ በላይ የነበረው ህዝብ ኑሮን ሳይኖር በከፍተኛ ደረጃ ከተበዘበዘ በኋላ መሰረት የጣለውን የኢኮኖሚ ዕድገት በኋላ ላይ ብቅ ያለው ትውልድ ነው መጠቀም የቻለው። በተለይም በአሜሪካንም ሆነ በአውሮፓ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሰፋ ያለ ምርት ማምረት የተቻለው ከ1950 ዓ.ም በኋላ፣ በተለይም የቴክኖሎጂ አብዮት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ነው።  ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ ግን በትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ መጽሀፍ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።

በአጠቃላይ ሲታይ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የቻለው በአንድ በኩል በአገዛዞች የዕውቅ ፖሊሲ ሲሆን፣  ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ አገዛዞች በኢኮኖሚ ቀድመው የሄዱ አገሮችን ምስጢር ለማወቅ ሰላዮችን በመላክና ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅ ነው። እንደ አውሮፓ በመሳሰለው ተጠጋግተው በሚኖሩ አገሮች ውስጥ ደግሞ በቀላሉ ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን መቅዳትና ማስተላለፍ(Knowledge Transfer) ስለሚቻል እንደ ጀርመን የመሳሰሉት ኋላ-መጥ አገሮች በቀላሉ በቴክኖሎጂ ሊያድጉ ችለዋል። በመንግስታት በዕውቅ ተግባራዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊስዎችና የዕውቀት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሸጋገር በየአገሮች ውስጥ ግለሰብአዊ ፈጣሪዎችን (Pioneer Spirit) እንደ አሸን እንዲፈልቁ አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። በሌላ ወገን ደግሞ ፊዩዳላዝም ከሃይማኖት ጋር በማበር የንግድ እንቅስቃሴን፣ ፈጠራንና የቴክኖሎጂን ዕድገት እንዳይኖር እንቅፋት በተፈጠረበት እንደስፔይንና ፖርቱጋል የመሳሰሉ አገሮች ከጎረቤት አገሮቻቸው በቀላሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመኮረጅ አልቻሉም። ከውስጥ የአስተሳሰብ ነፃነትን አፍነው ይዘው ስለነበር የተሻለ ዕውቀት የነበራቸው እንደ አይሁዲዎች የመሳሰሉት ወደ ሆላንድና ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ እንግሊዝ በመሰደድ ነው ዕውቀታቸውን በማስፋፋት ለኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ሊጥሉ የተቻሉት። በተለይም ለእንግሊዝ የኢኮኖሚ ዕድገትና በኢንዱስትሪ አብዮት ወደፊት መግፋት በስፔይን ወረራ የተነሳ ከሆላንድ ሸሽተው የሄዱ ምሁራኖችና የንግድ ሰዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረጋቸው የተነሳ ነው።

ወደ ቻይና ስንመጣ ቻይና በተደጋጋሚ በውጭ ኃይሎች በእንግሊዝ፣ በጃፓንና በፈረንሳይ ጦርነት ተከፍቶባታል። በዚያን ወቅትም ሆነ ፊት የተለያዩ የፊዩዳል ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ህብረተሰብአዊና የኢኮኖሚ ግንባታ እንዳይካሄድ ዕንቅፋት ፈጥረው ነበር። በዚህ ላይ ቀደም ብሎ የቻይና አገዛዞች ገበያውን ለውጭ ኃይሎች ክፍት ባለማድረጋቸው ምክንያት የተነሳ የእንግሊዝ ነጋዴዎች ገበያውን በኦፒየም ስላጥለቀለቁት የቻይና አገዛዝ በገበያ ላይ የሚዘዋወረውን ኦፒየም መንጠቅ ጀመረ። በዚህ የተናደደችው እንግሊዝ በቻይና ላይ በ1839 ዓ.ም ጦረነት ከፈተች። ጦረነቱም ሶስት ዓመት ያህል ፈጀ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታና ቀደም ብሎ በ1912 ዓ.ም የተጀመረው የሪፑብሊክ ምስረታ መስመር ለመያዝ ባለመቻሉ በ1921 ዓ.ም የኮሙኒስት ፓርቲ ተመሰረተ። በ1937 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ጃፓን ሁለተኛውን ጦርነት በቻይና ላይ ስለከፈተች ስልጣንን የያዘው የኮሚንታግ ወይም የናሺሊስቱ አገዛዝ ከኮሙኒስቶች ጋር በመተባበር በጃፓን ላይ ድል ከተቀዳጀ በኋላ የኮሙኒስት ፓርቲ በናሺናሊስት ፓርቲ የሚመራውን አገዛዝ ካባረረ በኋላ በ1949 ዓ.ም ስልጣንን ሙሉ በሙሉ  ለመቆጣጠር ቻለ። የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ስልጣንን ሲጨብጥ በጊዜው 500 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በቻይና ምድር ይኖር ነበር። ስለሆነም ይህንን ያህል ህዝብ አስተባብሮ አዲስ ስርዓት ለመገንባት አስቸጋሪ ነበር። የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ከእነስታሊን ጋር የነበረውን ግኑኘነት ካቋረጠ በኋላ በራስ ላይ መተማመን (Self-Reliance)የሚለውን የኢኮኖሚ ግንባታ በመከተል በአጭር ጊዜ ውስጥ ቻይናን የኢንዱስትሪ ባለቤት ለማድረግ የተወሰደው እርምጃ የእርሻውን መስክ ይህንን ያህልም አትኩሮ ስላልተሰጠው በጊዜው ወደ ሰላሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በረሃብ እንዲሞት ተደረገ። ይሁንና ከዚህ ስህተት የተማረው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማኦ ሴቱንግ እስከሞቱ ድረስ የማይናቅ የድርጅታዊ ስራና የኢኮኖሚ ግንባታ ለማካሄድ ችሏል። ራሳቸው የቻይና ተመራማሪዎች እንደሚሉት ህዝቡን ማስተባበርና ድርጅታዊ መልክ ለመስጠት የተቻለው ከ1949-1978 ዓ.ም ባለው ጊዜው ውስጥ ነው። ማኦ ሴቱንግ ከሞቱ በኋላ እነ ዴንግሲያዎ ፒንግ አራቱ ባንዶች በመባል የሚታወቁትን ኃይሎች ከስልጣን ላይ ካወረዱ በኋላ አራት የዘመናዊነትን ፖሊሲ በመከተል ነው ኢኮኖሚውን መገንባት የጀመሩ። በተለይም የነፃ ገበያ ዞን በመክፈትና አመቺ ሁኔታዎችን ለውጭ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች በመክፈት በዚያው መጠንም የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ቴክኖሎጂዎችን መኮረጅ ቻለ። ወደ ቻይና የመጡትንም ትላልቅና ማዕከለኛ ኩባንያዎች በአሜሪካን መንግስት ታዘው ሳይሆን ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በመነሳት ብቻ ነው። 1ኛ) የቻይና አገዛዝ የከፈተውን ዕድል በመጠቀም በርካሽ የማምረቻ ዋጋ፣ በተለይም የሰውን ጉልበት በመጠቀም ምርታቸውን እናመርታለን ብለው በማሰብ ብቻ ነው። 2ኛ) የቻይና ገበያ ገና በማደግ ላይ ያለ ስለነበር የሚያመርቱትን ምርት ቻይናና በአካባቢው አገሮች ለመሸጥ እንችላለን ብለው በማሰባቸው ነው። ይህም ማለት ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የመግዛት ኃይሉ ሲያድግ በዚያው መጠንም የትርፍ ትርፍ ለማካበት እንችላለን የሚል ግምት ነበራቸው። የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም ከተለያዩ አገሮች ወደ ቻይና ሲመጡና ምርት እንዲመረት ሲያደርጉ ቻይና ይህንን ዕድል በመጠቀምና ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅ መንጥቃን ትሄዳለች ብለው በፍጹም አልገመቱም ነበር።  ዮናስ ብሩ በተሳሳተ መልክ ያቀረበው በዚህ ዐይነቱ የቻይና የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የአሜሪካን ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝና የጃፓንም ኩባንያዎች ተሳትፈዋል። ለምሳሌ ሲሜንስ የሚባለው ትልቁ የጀርመን ኩባንያ ከአሜሪካኑ ጄኔራል ኤሌክትሪክ የተለያዩ የቤት ዕቃዎችንና የኤሌክትሮንኪስ ምርቶችን ከሚያመርተው ጋር የሚወዳደረው በቻይና ምድር ልዩ ልዩ የኤሌክትሮንክስ ዕቃዎችን፣ የልብስ ማጠቢያና የቤት ዕቃ ማጠቢያ ማሽኖችንና ሌሎችንም እዚያው ቻይና ውስጥ በማምረት ለቻይና ገበያና ለዓለም ገበያም ለማቅረብ ችሏል። እንዲሁም ትላልቅ የጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያዎች፣ እንደመርቼዲስ፣ ቮልስዋገን፣ አውዲና ቤኤም ደብልዩ የመሳሰሉት የመኪና አምራች ኩባንያዎች ቻያና ውስጥ በማምረት መኪናዎቻቸውን ቻይናና ሌሎች አገሮችም ይሸጣሉ። ይህም ማለት በቻይና የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ዮናስ ብሩ ሊያሳምነን እንደሚሞክረው ቻይና ከአሜሪካን ጋር “በወዳጀቷ” ብቻ ሳይሆን ይህንን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የቻለችው ከተለያዩ የካፒታሊስት አገሮች የመጡ ትላልቅ ኩባንያዎችም በመሳተፋቸው ነው። ግኑኘነቱም የወዳጅነት ሳይሆን ከላይ እንዳልኩት በርካሽ የሰው ጉልበት ለማምረትና እያደገ ሊመጣ የሚችለውን የሰፊውን ህዝብ የመግዛት ኃይል ለመጠቀምና የትርፍ ትርፍ ለማካበት ሲባል ብቻ ነው። ከአሜሪካንም ሆነ ከጀርመን፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ የሄዱና ኩባንያዎችን ቻይና ውስጥ የተከሉት በየመንግስቶቻቸው ትዕዛዝና  ፈቃድ ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ብቻ ነው። ከዚህም በላይ የዮናስ ብሩ አባባል ከካፒታሊዝም ሎጂክ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም። ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ የሚስፋፋው በተመሳሳይ ሁኔታ አይደለም። በቻይና ውስጥ የካፒታሊስት አገሮችን ኩባንያዎች ተሳትፎና በአፍሪካና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያላቸውን ተሳትፎ ጠጋ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ ትልቅ ልዩነት እናያለን። ትላልቅ የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ ኩባንያዎች ቻይና ውስጥ በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ምርት ሲያመርቱና የቴክኖሎጂ ልውውጥ አንዲኖር ሲያደርጉ፣ በአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አግሮች ውስጥ ይህንን መንገድ በፍጹም አይፈቅዱም። የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ ትላልቅ ኩባንያዎች በአፍሪካ ውስጥ ተሳትፎ የጥሬ-ሀብትን ለማውጣትና ሳይፈበረኩ ወደ ውጭ ለማውጣት ብቻ ነው። የእርሻ መስኩንም ስንመለከት በአበባ ተከላና ለውጭ ገበያ በሚሆኑ ምርቶች ላይ ብቻ ነው የሚሰማሩት። ከዚህ ዐይነቱ አጭር ገለጻ ስንነሳ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ መልክና በተመሳሳይ ጥልቀት በፍጹም አይስፋፋም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ያልተስተካከለ ዕድገትና በተለይም በአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገር ህዝቦች ያለው የኑሮ ሁኔታ የሚያረጋግጠው የካፒታሊዝም ዋናው ተልዕኮ ሁሉንም አገሮች በተስተካከለ መልክ ማሳደግ እንደማይችልና የካፒታሊስቶች ፍላጎትም እንዳልሆነ ነው።

ይህንን ትተን  ወደ ቻይና የኢኮኖሚ ፖሊስ ጋ ስንመጣ የቻይና አገዛዝ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ሳይሆን መከተል የጀመረው ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግና ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅና በማሻሻል ነው ውጤታማ ለመሆን የበቃው። የኋላ ኋላ ላይ የቻይና ኢኮኖሚ እየጠነከረና እየሰፋ ሲመጣ የውጭ ኢንቬስተሮችን ያስገድድ የነበረው ቴክኖሎጂዎችን ከእነ ዕውቀታቸው(Know-how) ጭምር ተግባራዊ እንዲያደርጉና፣ በተለይም የምርምርና የዕድገት ማዕከል እንዲከፍቱ በማድረግ ነው በሰላሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቻይና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለችው። ስለሆነም ዮናስ ብሩ ሊያሳምነን እንደሚሞክረው ቻይና ከአሜሪካን ጋር መወዳጀት ስለጀመረች ሳይሆን ኢኮኖሚዋን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የቻለችው ጥበብ የተሞላበት ፖሊሲ በመከተሏና የመንግስታዊ መዋቅሯን በማጠንከሯ ብቻ ነው። በዚህ ላይ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመቹ ዩኒቨርሲቲዎችና መጻህፍት ቤቶች በየቦታው ለመስፋፋት በመቻላቸው የቻይና የኢኮኖሚ ዕድገት በዕውቀት ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል። በሌላ አነጋገር፣ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ምስጢርና አስፈላጊነት የተረዳ አገዛዝ ካለ ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረ ኢኮኖሚ መገንባት የሚችለውና ህዝቡንም ከድህነት ለማላቀቅ የሚቻለው። ቻይና ይህንን መንገድ በመከተል ነው ዛሬ ወደ ኃያል መንግስትነት ለመለወጥ የቻለችው።  በሌላ ወገን ግን ዛሬ የሚታየው የቻይና የኢኮኖሚ ዕድገትና በዓለም ገበያ ላይ ምርቶችን ማራገፍ ወደ ውስጥ የቻይና ሰራተኛና ሰፊው ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍሉ አስገድዷቸዋል። በአፍላው ወቅት የቻይና ወዝአደር በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝ ነበር። ለመብቱም መታገል ስለማይችል ዝም ብሎ ይበዘበዝ ነበር። የኋላ ኋላ ላይ ብዝበዛው ሲበዛበት በየቦታው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ተቃውሞውን ያሰማ ነበር። ከዚህም በላይ በየቦታው ያሉት የቻይና የአገዛዝ መዋቅሮችና አስተዳዳሪዎች ንቃተ-ህሊናቸው የዳበረ ስላልነበር የአካባቢ መበከል በግልጽ ይታይ ነበር። ከፋብሪካ በሚወጡ መርዞች ወንዞችም ይበከሉና ይቆሽሹ ነበር። በተጨማሪም አዲስ መጤ በሆኑ ከበርቴዎች ሰፊው ህዝብ ከቤቱ በመፈናቀል አዳዲስና ትላልቅ ህንፃዎች ይሰሩ ነበር። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በቻይና ምድር ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና፣ የባህልና የማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ችሏል። የስራ መስክ ፈላጊውም ሰራተኛ ከቤተሰቡ በመነጠል አንድ ሺህና ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለበት ቦታ እንዲኖር ለመገደድ በቅቷል። ይህና አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም ከፍተኛ ቀውስ በማስከተሉ የተነሳ ራሱን የሚገድለው ቻይናዊ ቁጥሩ ከፍ ያለ ነበር። ስለሆነም በቻይና ምድር ተከታታይነት ያለውና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊታይ የቻለው ከፍተኛ መስዋዕትነትን በመከፈል ብቻ ነው።

ለማንኛውም በአንድ አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮሚ ዕድገት እንዲመጣ ከተፈለገ የግዴታ የአገር ወዳድነት ስሜት ያለውና በጥሩ ዕውቀት የታነፀ አገዛዝ ወሳኝ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ደረጃ በደረጃ መወሰድ ያለባቸውን ነገሮች ማወቅ ያለበት አገዛዝ መሆን አለበት። በሶስተኛ ደረጃ፣ የግዴታ በውጭ ኃይል ላይ ጥገኛ መሆን የለበትም፤ ወይም አመኔታ መጣል የለበትም። በአንድ አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በራስ ላይ ዕምነት ሲኖርና ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ጉልበት  በማንቀሳቀስ  ብቻ  ነው። ይህ ማለት ግን ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ መኮረጅና ወይም ማስገባት አያስፈልግም ማለት አይደለም። አንድ አገዛዝና ምሁራዊ ኃይል ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቹ ቴክኖሎጂዎች የትኞቹ እንደሆኑ በሚገባ ማወቅና መኮረጅ አለበት፤ ይህንንም ማስፋፋትና ማዳበር መቻል አለበት። በዚህ ላይ ለምርምርና ለዕድገት የሚያመቹ የቴክኖሎጂ ማዕከሎችን ማቋቋም አለበት። በአጭሩ አንድ አገር ቀድሞም ሆነ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ ለማደግ የምትችለው በዕውቅ ላይና በዕቅድ በመመስረት ብቻ ነው። አንድ አገር በነፃ ንግድ አማካይነት ወይም ገበያዋን ለውጭ ኢንቬስተሮች ለሚባሉት ክፍት በማድረጓ በፍጹም ለማደግ አትችልም። ምክንያቱም የውጭ ኢንቬስተሮች የሚባሉት አንድን አገር በኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚመጡ ሳይሆን የጥሬ-ሀብት ዘረፋ ላይ ለመሰማራትና እሱን አውጥቶ ሳይፈበርኩ ወደ ውጭ ለማውጣት ስለሆነ ነው። በቀጥታም ኢንቬስትሜንት(Direct Investmient) በሚባለውም አንድ አገር በኢኮኖሚ ልታድግ አትችልም። ምክንያቱም የቀጥታ መዋዕለ-ነዋይ የሚባለው ነገር ዕውቀት የሚተላለፍበት ሳይሆን ዋናው ዓላማው ርካሽ ጉልበትን ለመጠቀምና ለውጭ ገበያ በሚያመች የጥሬ-ሀብትና የምርት ክንዋኔ ላይ ብቻ ለመሰማራት ስለሆነ ነው። በአጭሩ አንድ አገር የኃያል መንግስት ጥገኛ በመሆኗ ወይም ትላልቅ ኩባንያዎች ቢመጡና መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ ቢችሉ ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ በመገንባት ህዝቧን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በፍጹም ልታላቅቅ አትችልም።

ይህንን ካየንና በሚገባ ካጤን በኋላ በአጠቃላይ ሲታይ በሶስተኛው ዓለም፣ በተለይም በካፒታሊስት አገሮችና በአፍሪካ አገሮች የነበረውንና ያለውን ግኑኘነት እንመልከት። ለምሳሌ አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም አነሰም በዛም ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ታይዋንና ኋላ ላይ ደግሞ ቻይና ውስጥ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ ሲፈቅዱና ዝምብለው ሲመለከቱ ለምንስ አፍሪካን አልረዱም? ወይስ አንዳንድ አፍሪካ አገሮች ሙከራ ሲያድርጉ ለምን ዝምብለው አልተመለከቱም? የሚለውን እንመርምር።

በእኛ በኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ ለውይይት ያልቀረበና ለማጥናትም ሙከራ ያልተደረገበት ነገር በተለይም የባርያ ንግድና የቅኝ ግዛት አስተዳደር በአፍሪካ የህብረተሰብ አወቃቀር ላይ ያላቸውን ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚመለከት ጉዳይ ነው። በታሪክና በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ እንደታየው እያንዳንዱ አገር የዛሬው የዕድገት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የራሱ የሆነ አነስተኛ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ የባህል ዕድገት ነበረው። አውሮፓውያን ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የአገዛዝ መዋቅር ነበራቸው። በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚና የንግድ ልውውጥም ነበራቸው። በዕደ-ጥበብ ሙያም መጥቀው የሄዱና ከተማዎችንም መስርተው ነበር። አውሮፓውያኖች በወረራ መልክ ወደ አፍሪካ ሲመጡ ለብዙ መቶ ዓመታት የዳበሩ የባህልና የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረቶችን ነው ማፈራረስ የጀመሩት። በተለይም በባርያ ንግድ አማካይነት ወጣቶችንና ሊሰራ የሚችለውን አሟጠው ከአፍሪካ ምድር ስለወሰዱ በየአገሩ የቀረው ሊሰራ የማይችል የአረጀ የሰው ኃይል ነበር።በዚህም ምክንያት የተነሳ የመጀመሪያው የአፍሪካ የህብረተሰብ አወቃቀርና የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት የሆነው ሊጨናገፍ ቻለ። በሁለተኛ ደረጃ፣ በቅኝ-አገዛዝ ዘመን የሆነው ሁኔታ ነው። የአውሮፓ አገሮች ወደ አፍሪካ ሲመጡ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ለመገንባትና በቴክኖሎጂ ለማሳደግ ሳይሆን የጥሬ-ሀብታቸውን ለመበዝበዝ ነው። በተለይም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ዘልቀው የቀሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማገድ ገበሬው ለውጭ ገበያ ብቻ በሚቀርብ ሰብል ላይ ብቻ፣ ለምሳሌ እንደ ሻይ፣ ቡናና ኦቾሎኒና እነዚህን በመሳሰሉት ላይ ብቻ እንዲሰማራ አስገደዱት። የአውሮፓ የቅኝ አገዛዞች የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በቆዩበት ዘመናት ከተማዎችን አልገነቡም። የባቡር ሃዲድም አልዘረጉም። የገበያ አዳራሾችን አልመሰረቱም። ለቴክኖሎጂ መስፋፋት መሰረት የሚሆን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን አላስፋፉም፤ ምርምርና ዕድገት እንዲስፋፋም አመቺ ሁኔታዎችን አልፈጠሩም። የሙያ ማስለጠኛ ማዕከሎችንም አልከፈቱም። በአጭሩ አፍሪካን አቀጭጨው ነው የሄዱት። ይህ ዐይነቱ ሁኔታና የተዘረጋው የተዘዋዋሪ የቅኝ-ግዛት(Neo-Colonial Structure) አስተዳደርና የመንግስት መኪና ነው እስከዛሬ ድረስ ዘልቆ በመቅረት በአፍሪካ ምድር ውስጥ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት ለመሆን የቻለው። ዛሬም ያለው ትግል ይህ ዐይነቱ የካፒታሊስትና የአፍሪካ አገሮች ግኑኘት( Centre-Periphery Relationship) እንዲቀጥል ነው የካፒታሊስት አገሮች አጥብቀው የሚሰሩት።

አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ነፃነታቸውን ተቀዳጁ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በራሳቸው ተነሳሽነት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣት ወደ ውስጥ ያተኮረ ኢኮኖሚ መገንባት አልቻሉም። ሁሉም ነገር ከውጭ ተዘጋጅቶ ይመጣ ስለነበር ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደግሞ ሰፋ ላለ የውስጥ ገበያ ዕድገት የሚያመች አልነበረም፤ አይደለምም። ለሳይንስና ለተክኖሎጂ ዕድገት መሰረት ሊጥል የሚችል አልነበረም፤ አይደለምም። በአጭሩ አፍሪካን የጥሬ-ሀብት አምራች አህጉር ብቻ አድርጎ የሚያስቀር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ተግባራዊ ለመሆን የቻለውና አሁንም የሚተገበረው። አንዳንድ አገዛዞች በራሳቸው ጥረት ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ መከተል ሲጀምሩ የመንግስት ግልበጣ ይደረግባቸው ነበር። አንዳንድ መሪዎችም ይገደሉ ነበር። ለምሳሌ ፕሬዚደንት ሙሀመር ጋዳፊ አፍሪካ የግዴታ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ያስፈልጋታል፤ ይህንን ፖለሲ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በወርቅ የተደገፈ ወርቅ ዲናር (Gold Dinar) የሚባል ገንዘብ መታተም አለበት ብለው ሲያውጁ በዚህ የተደናገጡ የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችና አሜሪካም ጭምር፣ በተለይም ፈረንሳይና አሜሪካ ሰበብ ፈልገው ሊቢያ በመግባት ፕሬዚደንት ጋዳፊን አሳድደው በመግደል አፍሪካን በኢንዱስትሪ ተከላ ለማበልጸግ የታለመው ህልም እንዲጨናገፍ ለማድረግ ችለዋል። ሳንካራም ነፃ ኢኮኖሚ እገነባለህ ስላለ ነው ለፈረንሳይ በተገዛ ወታደር ሊታረድ የቻለው። የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለ በኋላ ከስድሳ በላይ የሚበልጥ የመንግስት ግልበጣ ተካሂዶባቸዋል። በአንፃሩም ለካፒታሊስት አገሮች የሚያመቹ አገዛዞች እንዲቀመጡ ተደርገዋል። በዚህ መልክ ብዝበዛውና ኋላ-ቀርነቱ መቀጠል አለበት። ይህንንም የሚያቀነባብሩት የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ፣ የእንግሊዙ የስለላ ድርጅትና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅቶች ናቸው።  ወደ ፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ወደነበሩት አገሮች ጋ ስንመጣ ፈረንሳይ እስካሁን ድረስ አስራ አራት የሚሆኑ የአፍሪካ አገሮችን ልክ እንደ ቅኝ ግዛቶቿ አፍና ነው ይዛ ለመቆየት የቻለችው። አንዳቸውም አገር የራሱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ አይፈቀድለትም። የአስራአራቱም የፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ-ግዛቶች ገንዘባቸው ቀድሞ ከፈረንሳይ ገንዘብ ጋር፣ አሁን ደግሞ ከኦይሮ ጋር ስለተያያዘ ከረንሲዎቻቸውን እንደፈለጋቸው ማሻሻል(Manipulate) አይችሉም። ወደ ውጭ ከሚልኩት ምርትና ከሚያገኙት የውጭ ከረንሲ ደግሞ 60% የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪና ወርቅ የፈረንሳይ ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ አለባቸው። በዚህ መልክ ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿን ቆልፋ በመያዝ ወደ ውስጥ ያተኮረ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡና ነፃም እንዳይወጡ ለማድረግ ችላለች።

ይህንን ከተመለከትን በኋላ የካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም አሜሪካ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የመሰረተቻቸው ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሚባል ስም የተሰጣቸው እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF)  የዓለም ባንክ የመሳሰሉት የአፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚ እንዳያድጉና ህዝቦቻቸውን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት እንዳይላቀቁ በማድረግ ከፍተኛ ደባ ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ነው። በተለይም በኢኮኖሚ ሙያ ስለጠን የሚሉ የአፍሪካን ምሁራንን በመቅጠርና ለአፍሪካ መንግስታት የተሳሳተ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ ምክር በመስጠት በየአገሮች ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረና የተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመጣ ለማድረግ በቅተዋል። በተለይም የአፍሪካ የመንግስታት አወቃቀር፣ ማለትም የሚሊታሪው፣ የፀጥታው፣ የሲቪሉና የቢሮክራሲው መዋቅርና ሰዎችም በተሳሳተ ትምህርት የሰለጠኑና በአስተሳሰባቸውም ወደ ኋላ የቀሩ በመሆናቸው የካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም አሜሪካን እነዚህን በመጠቀም በየአገሮች ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረ ዕድገት እንዳይመጣ ለማድረግ በቅታለች። ባጭሩ አሜሪካና ግብረ-አበሮቿ በአፍሪካ ምድር የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ሁኔታ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቻይና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይደገም አጥብቀው ይሰራሉ። ከዚህ ውስጥ አንደኛው ተንኮላቸው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ማድረግና ህዝቡን በጦርነት መወጠር ነው። እንደ እኛ ያለውን አገር ደግሞ በጎሳና በሃማኖት በመከፋፈል የድህነትና የኋላ-ቀርነቱ ዘመን እንዲራዘም ማድረግ ነው። በዚያው መጠንም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያደሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያኖችን እያሰለጠኑ ብልግናን ማስፋፋት ነው። ለወጣቱና ለሰራ ፈላጊው ሰፊ ህዝብ የሚሆንና በቂም የስራ መስክ ሊከፍቱ የሚችሉ በትናኝሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከማትኮር ይልቅ ሆቴልቤቶችን በመክፈት የብልግና ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ነው። ሆቴልቤቶችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ደግሞ በራሳቸው ሀብት ፈጣሪዎች አይደሉም። እንደሚታወቀው በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ስርዓት ያለው የኢንዱስትሪ ተከላና፣ ይህ መስክ ከእርሻውና ከሌሎች የጥሬ-ሀብት አምራች መስኮች ጋር ሲያያዝ ብቻ ነው ብሄራዊ ሀብት ሊፈጠር የሚችለው። ስለሆነም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ አፈ-ቀላጤዎችን በየአገሩ በማሰማራትና የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚሉትን ነገር ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግና በማስገደድም በአፍሪካ ምድርና አገራችንም ውስጥ ሰፊውን ህዝብ ሊያስተሳስርና ፈጣሪ ሊያደረግው የሚችል ሰፋ ያለ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ እንዳይካሄድ መንገዱን ሁሉ ዘግተዋል።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ ዮናስ ብሩ እንደሚለን ኢትዮጵያ የእሜሪካን ጥገኛ ብትሆን በኢኮኖሚ ማደግ ትችላለች የሚለው አስተሳሰብ በፍጹም የሚሰራ አይደለም። በታሪክም አልተረጋገጠም;፡ በተለይም ብዙ የሚወራለትን የአሜሪካንንና የኢትዮጵያን ግኑኘነት ስንመለከት በአሜሪካንና በአፄ ኃይለ ስላሴ አገዛዝ መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት ነበር። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ይህንን በመጠቀም በጊዜው ስልጣን ላይ የነበረውን የአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝና አስተዳደር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርግ ከመምከርና ከተማዎችንና መንደሮች የሚያይዙ የባቡር ሃዲዶችን እንዲዘረጉ ከመገፋፋት ይልቅ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በመምከር ነው ሁኔታዎችን ማዘበራረቅ የቻለው። እንደምናውቀው የአፄው አገዛዝ በጭቆና መኪናው ከመፈርጠሙ በስተቀር ህዝባችንን ርስ በርሱ ሊያስተሳስረውና በራሱም ላይ እንዲተማመን የሚያደርገውን ጠንካራ የሆነ ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አልቻለም። ስለሆነም ነው በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን በከተማና በገጠር መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ይታይ የነበረው። በተለይም ለአዲስ አበባ ብቻ ትኩረት በመስጠት ነው ወደዚያ የተማረ ኃይልና ሀብትም ሊፈስ የቻለው። ራሱም አዲስ አበባም በተስተካከለና በዕቅድ የተገነባ ከተማ አልነበረም። የተተከሉትም ኢንዱስትሪዎች የተወሰኑ የፍጆታ ምርቶችን የሚያመርቱና ለተወሰነውም የህብረተሰብ ክፍል ብቻ  የሚያቀርቡ ስለነበሩ የመባዛትና የማደግ አቅም አልነበራቸውም፤ እንዲሁም ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ለመክፈት የሚችሉ አልነበሩም። ይህ ዐይነቱ ደካማ የኢንዱስትሪ ተከላ የተዘበራረቀ ሁኔታ በመፍጠሩ የተነሳ ቴክኖሎጂዎችን ሊፈጥር የሚችል መንፈሱ የጠነከረ አዲስ ፈጣሪ የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። በአንፃሩ ኮምፕራዶር ቡርዧዋዚ ብለን የምንጠራው በኤክስፖርትና በኢምፖርት ላይ ብቻ የተሰማራ የነጋዴ የህብረተሰብ ክፍል ነው ብቅ ለማለት የቻለው። በአጭሩ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን አንድ የተሟላ ከተማ መገንባት አልተቻለም። ትናኝሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችንንም ማስፋፋት አልተቻለም። የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ማዕከልም አልተከፈተም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰፋ ያለ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ መገንባት አልተቻለም። በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊስና በካፒታሊዝም ወደ አገራችን ዘልቆ መግባት የተነሳ ሊስፋፉ የቻሉት የተዝረከረኩ የኢኮኖሚ ምርቶችና የንግድ ልውውጥ ነው። እነዚህም ኢንፎርማል ኢኮኖሚ በመባል ይታወቃሉ። የሱቅ በደረቴ፣ የተዝረከርኩ የገበያ ቦታዎች፣ ጠላና ጠጅ ቤቶች፣ ሻይ ቤቶችና የሴተኛ አዳሪ መስፋፋት ከዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የሚያያዙ ናቸው።

አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ አሜሪካና ግብረ-አበሮቹ የማጨናገፍ ስራ ነው መስራት የጀመሩት። የርስ በርስ ጦርነት እንዲካሄድ ነው የተለያዩ ተስፈንጣሪ ኃይሎችን በማስታጠቅ ጦርነቱ እንዲፋፋም ያደረጉት። የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ወያኔን ስልጣን ላይ ካወጡ በኋላ ለሳይንና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲተገበር ከመምከርና ከመገፋፋት ይልቅ ለዘረፋ የሚያመችና ሰፊውን ህዝብ ደግሞ የባሰ ደሃ የሚያደርግ የተቋም ማስተካከያ ፖሊሲ(Structural Adjustment Programs) ብለው የሚጠሩትን ነው ተግባራዊ እንዲሆን ያስገደዱት። ይህም ፖሊሲ፣ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልሆነና በማንኛውም የካፒታሊስት አገርም ሆነ፣ በጃፓንና በደቦቡ ኮሪያና አሁን ደግሞ በቻይና ምድር ተግባራዊ ያልሆነ ነው። ይህ ከሆነ በምን ተዓምር ነው ዮናስ ብሩ እንደሚለን ኢትዮጵያችን  የአሜሪካን ጥገኛ ብትሆን በኢኮኖሚ ማደግ የምትችለው? አሜሪካ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን፣ በኋላ ላይ ደግሞ በወያኔ 27 ዓመት የአገዛዝ ዘመን፣ አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ እስካሁን ጌ ድረስ ሶስት አገዛዞች  በአሜሪካን ይደገፉ ከነበርና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ካልቻሉና ሰፋ ያለ ወደ ውስጥ ያተኮረ የውስጥ ገበያ እንዲዳብር ለማድረግ ካልቻሉ በምን ተዓምር ነው አሁን ማድረግ የሚችሉት? የአቢይ አሀመድ አገዛዝስ ከማን ትዕዛዝ እየተቀበለ ነው የኢኮኖሚ ፖልሲ የሚሉትን እንዲተገበር የሚያደርገው? የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ሚና በኢትዮጵያ ምድር ምንድን ነው? ዮናስ ብሩ እነዚህን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ መቻል አለበት። ከዚህ በላይ  ዮናስ ብሩ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ሲያወራ ምን ማለቱ እንደሆነ በፍጹም ግልጽ ለማድረግ አልቻለም። ለመሆኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ አገዛዞችና በአሜሪካን መሀከል የነበረውን ግኑኝነት በሚገባ አጥንቷል ወይ? ከዚህም ባሻገር የአሜሪካንንና የተለያዩ የካፒታሊስት አገሮችና ተቋሞቻቸውን በአፍሪካ ምድር ውስጥ ያላቸውን አሉታዊ ሚና በሚገባ አጥንቷል ወይ? አሜሪካስ በምን ተዓምር ነው በተለይም ለኢትዮጵያ ፍቅር የሚኖራትና በኢኮኖሚም በተሟላ መልክ እንድታግዝ ማድረግ የሚቻለው? የትኛውንና ምንስ ዐይነት አገዛዝ ቢኖር ነው ለዕድገት የሚያመች ሁኔታ ልትፈጥር የምትችለው? የአሁኑ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ስልጣን ላ እያለ ወይስ እሱ ከስልጣን ላይ ወርዶ በአዲስ ሲተካ ነው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ የምትፈቅድልን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚገባ መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል

ዮናስ ብሩ በታሪክና በሳይንስ ያልተደገፈ ውዥንብር ከመንዛቱ በፊት የዓለምን ታሪክ፣ በተለይም የካፒታሊዝምን ዕድገትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በምን መልክ እንደተስፋፋና እንደሚስፋፋ በሚገባ ማጥናት አለበት። በተለይም በፖለቲካ ስም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቹ የሚሰራውን ውንብድናና አገሮች እንዳይረጋጉ የሚሸርቡትን ሴራ በሚገባ ማጥናት አለበት። በተለይም የዛሬ አርባ ዓመት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደመመሪያ መወሰድ ከተጀመረ ወዲህ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ በሚቆጣጠሯቸው የዓለም አቀፍ የሚባል ስም በተሰጣቸው ተቋማት አሳበው በተለይም በአፍሪካ ምድር ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሊያዳብር የማይችል ወይም መሰረት ያላደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት ተግባራዊ እንዲሆን ነው አገዛዞች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያደርጉት። በዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በአጠቃላይ ሲታይ በግሎባላይዜሽን ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ ዘራፊና ጨቋኝ አገዛዞች ሊደልቡና ህዝቦቻቸውን አቅመ-ቢስ ለማድረግ ችለዋል። በየአገሮች ውስጥ የንዑስ ከበርቴው ፋሺዝም ስልተስፋፋና ይህ ዐይነቱ አገዛዝም የሚያደርገውን ስለማያውቅ በአገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህል፣ የስነ-ልቦና ቀውስና የእካባቢ ቀውስ ይታያል። ይህንን ለማስተካከል ወይም ለማረም የሚችል ምሁራዊ እንቅስቃሴ በየአገሮች ስለሌለ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር፣ በተለይም አገራችን የማንም መጨፈሪያ ለመሆን በቅታለች። ስነ-ምግባርና ሞራል እንዳለ ስለወደሙ በአጠቃላይ ሲታይ ጋጠወጥነት ተስፋፍቷል ማለት ይቻላል። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ከአሜሪካን ጋር ብትወዳጅ በኢኮኖሚ ታድጋለች ብሎ የተሳሳተ አስተሳሰብ መንዛት ተጨባጭ ሁኔታዎችን በሚገባ አለማንበብና የዓለም ሁኔታም ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ በቅጡ አለመረዳት ነው።

ዮናስ ብሩ ባለፉት አርባ ዓመታ በኒዎ-ሊበራሊዝምና በግሎባላይዜሽን ስም የተፈጸመውን ወንጀል ሳያጠናና ሳይገነዘብ በጥሩ እንግሊዘኛ፣ ይሁንና እጅግ በተሳሳተ መልከ የሚያቀርበው የተሳሳተና ኢ-ሳይንሳዊ ጽሁፍ በጣም አደገኛ ነው። ዮናስ ብሩና ሌሎችን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አቀንቃኝ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ዐይነቱ አሳሳች አካሄድ መቆጠብ አለባቸው። ከአሜሪካን ጋር ብንወዳጅና ጥገኛ ብንሆን ዕድገትን እናመጣለን የሚለው ደካማ አስተሳሰብ የግዴታ ገደብ መያዝ አለበት። እንደዚህ´ ብለን የምናስብ ከሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ተቋሙ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) እየተመከረ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርገውና ህዝባችንን የሚያደኸየው ትርጉሙ ምን እንደሆነ በፍጹም አልገባንም ማለት ነው። ስለድህነትና ስለኢኮኖሚ ቀውስ እያወራን ለዚህ ዐይነቱ ቀውስ ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ በፍጹም የተረዳን አይመስለኝም።  በእኔ ዕምነት ዮናስ ብሩና ሌሎችም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ላይ ዕምነት ያላቸው ቴክኖክራቶችና ኢኮኖሚስቶች ነን የሚሉ ሁሉ የዓለምን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አወቃቀር በተሳሳተ መልክ በማንበብ ነው እዚህ ዐይነቱ ድምዳሜ ለመድረስ የቻሉት።  የምዕራቡን የካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም አሜሪካንን እንደ ቅዱስ በማየትና ዘረኝነትም የለም በማለትና በመጻፍ ነው በተለይም ታዳጊ ወጣቶችን የሚያሳስቱት። ከዚህም በላይ ዮናስ ብሩ ስለካፒታሊዝም ዕድገት በቂና ሳይንሳዊ ግንዛቤ ያለው አይመስለኝም። በእሱ ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በአቅራቢና በጠያቂ ህግ(The Law of Supply and Demand) ብለው በሚጠሩት፣ ይሁንና ደግሞ ከሳይንስ ውጭ በሆነ አስተሳሰብ ነው። ዮናስ ብሩ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢሌን ገብረመድህንና ዘመዴነህ ንጋት የሚባሉ ለዓለም ባንክና ለተለያዩ ተቋማት ሲሰሩ የነበሩና ቀድሞ የወያኔ አገዛዝ፣ አሁን ደግሞ የአቢይን አገዛዝ የሚያማክሩ ሁሉ አስተሳሰባቸው በተሳሳተ የነፃ ገበያ አስተሳሰብ የተቀረጸ ስለሆነ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶችን እያሳሳቱ ነው። ለዝንተ-ዓለማችንም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጥገኛና ደሃ ሆነን እንድንቀር አጥብቀው ይሰራሉ። በአንድ ወቅት ዮናስ ብሩ ራሱ የአቢይ አህመድ የኢኮኖሚ አማካሪ እንዲሆን ከተመረጡት ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ዘመደኔህ ንጋቱና ኤሌኒ ገብረመድህን ደግሞ ቀድሞ የወያኔ አገዛዝ ሲመክሩና የጥሬ ሀብትም እንዲዘረፍ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። በከፍተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ እንዲዘበራረቅ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ያደረጉ ናቸው። አሁን ደግሞ ኤሌኒ ገብረ መድህን አንድ አገር በኢኮኖሚ ለማደግ የምትችለው በስራ ፈጣሪ ነው እያለች ወጣቱን ታወናብዳለች። እንዴትና በምስን መልክ የስራ ፈጣሪ እንደሚፈጠር አትነግረንም። አገላለጿን ለተመለከተ ሴትየዋ ስለካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ዕድገትና፣ በተለይም ስለአነስተኛና ስለማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች አፀናነስና መዳበር ምንም ዕውቀት ያላት አይመስለኝም። ከዚህም በላይ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተደግፎ ስለሚንቀሳቀስ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ግንባታ ምንም የምትለው ነገር የለም። ከዚህ በተጨማሪ ሶስቱም ስለመንግስት አወቃቀርና በምንስ መልክ ቢዋቀር ሰፊውን ህዝብ ከድህነት ሊያላቅቀው ይችላል? የሚለውን ጥያቄ ሊያብራሩ አይችሉም። ባጭሩ መንግስት የሚባለውን አካል እንደማይነካ፣ እንደማይዳሰስና እንደማይሻሻል አድርገው ነው የሚወስዱት።  በስልጣን ላይ የሚወጡት ኃይሎች የሰለጠኑና ስለሰው ልጅና ስለ አገር በቂ ግንዛቤ ያላቸው መሆናቸውን በፍጹም አይገነዘቡም። ዮናስ ብሩ፣ ዘመዴነህ ንጋቱና ኤሌኒ ገብረመድህን ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትንና ጦርነትን የሚያስፋፋውን የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝምን፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምንና የተቋማቱን አስተሳሰብ ነው ነው የሚያስተጋቡት። በተለይም ኤሌኒ ገብረመድህን ተቀባብትና ተቆነጃጅታ በመምጣትና በመጠየቅ ወጣቱን እያታለለች ነው። ዘመደኔህ ንጋቱ ደግሞ የካፒታል ማርኬት ወይም ገበያ ያስፈልጋል እያለ እንደዚሁ ውዥንብር በመንዛት ላይ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በሌላ መልክም በተቀናጀና ስርዓት ባለው መልክ ልዩ ዐይነት የክሬዱት ሲይስተም ቢቋቋምና፣ በተጨማሪም ብዙ ገንዘብ ያላቸው አንዳንድ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ልዩ ዐይነት የቁጠባ ባንክ ውስጥ ቢያስቀምጡና ወለድም እየተከፈላቸው ገንዘቡ በዚህ መልክ ለኢንዱስትሪ ተከላ መስፋፋት ያለውን ሚናና ኃይል ሲያስረዳ አይታይም። የካፒታል ገበያ የሚባለው በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የተለመደው በተለይም በአሁኑ ወቅት የአየር በአየር ንግድ የተስፋፋበት ነው። ትላልቅ የማምረቻ ኩባንያዎች ከዚህ ዐይነቱ የካፒታል ገበያ ተጠቃሚ ሲሆኑ ትናንሽና ማዕከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትራዲሽናል በሆነ የባንኪንግ ሲስተም አስራር ነው ምርቶቻቸውን የሚያስፋፉት። ሌሎች መንገዶችም አሏቸው። ከዚህም በላይ የካፒታል ገበያ የሚባለው በኬንያና በደቡብ አፍሪካ የሚሰራበት ስለሆነ እነዚህን አገሮች ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በፍጹም አላላቀቃቸውም። በሌላ አነጋገር፣ በዕውቅ ለኢንዱስትሪዎች ተከላና መስፋፋት የማይውል የካፒታል ገበያ ትርጉም አይኖረውም። ከዚህም በላይ በመንግስት የሚደገፍ ምርምር ወይም ፈጠራ በማይካሄድበት አገር ውስጥ ኢኮኖሚው ማደግ አይችልም። ስለሆነም ኤሌኒ ገብረመድህንና ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚሉን አንድ አገር በስራ ፈጣሪና በካፒታል ገበያ በፍጹም ሊያድጉ አይችሉም። የዮናስ ብሩም ሆነ ሀለቱ ኢኮኖሚስቶች ነን ባዮች ሰፋ ላለ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታና፣ አንድ ህብረተሰብ በምን መልክ መያያዝ እንዳለበትና ፈጣሪም ሊሆን እንደሚችል በፍጹም አይነግሩንም። እነዚህ ኢኮኖሚስቶች ነን የሚሉ በአንዳቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ክርክር በሚደረግባቸው አማራጭ የኢኮኖሚ ዕድገት ክርክሮች ላይ ያልተሳተፉና ስለኢኮኖሚ ዕድገትም ሰፋ ያለ ጥናት ያላቀረቡ ናቸው። ስለሆነም ከእነዚህ ዐይነቶችናና ቀደሞ በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ከነበሩ አሳሳች ምሁራን መራቅና ምክራቸውንም አለመስማት ነው።

ለማንኛውም ሰለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ከጠቅላላው ህብረተሰብ ጋር የሚያያዝ መሆን አለበት። ኢኮኖሚ የሚያድገው ለማደግ ተብሎ ሳይሆን የግዴታ የእያንዳንዱን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላትና ከድህነትም በማላቀቅ ጤናማ ዜጋ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ከዚህም በላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጥቂቶቹን የሚያፈረጥም፣ አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ ደሀና አቅመ-ቢስ የሚያደርገው መሆን የለበትም። ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ከመንፈሳዊ፣ ከሞራልና ከስነ-ምግባር መጠንከርና መሻሻል ጋር የሚያያዝ መሆን አለበት። በአንድ አገር ውስጥ ጤናማ ህብረተሰብ የሚገነባው ኢኮኖሚያው ዕቅድ ከህዝብ ፍላጎትና ከመንፈሳዊ መበልጸግ ጋር ሊያያዝ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አመጽ በተስፋፋት ዘመን የግዴታ በአንድ አገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የህዝብን መንፈስ የሚያጠነክሩና ሰው መሆኑንም የሚያስገነዝቡ ሰፋ ያሉ ባህላዊ ክንዋኔዎችና ግንባታዎች መካሄድ አለባቸው። ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ከመንግስት መኪና አወቃቀር፣ ስልጣን ላይ ስለሚወጡ ኃይሎች ዕውቀትና የስልጣኔ ተልዕኮ፣ ስለማህበራዊ ሁኔታና ስለ ኢኮሎጂ ጉዳይ፣ በተለይም ታዳጊው ወጣት በምን መልክ መኮትኮትና ኃላፊነትም ተቀባይ ሊሆን እንደሚችል…ወዘተ… ወዘተ፤  በእነዚህ ነገሮች ላይ በቂ ምሁራዊ ክርክርና ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታችንን መወጣት የምንችለው። መልካም ግንዛቤ!!

 

                                                                                                                                                   fekadubekele@gmx.de

                                                                                                                                                www. fekadubekele.com

Literature

Chang Ha-Joon, Kicking Away the Lader, London, 2005

David S. Landes, The Unbound Prometheus: Technological Change and Industrial

                            Development in Western Europe from 1750 to the Present, UK, 2003

Davis S. Landes, The Wealth and Poverty of Nations, New York, 1999

Erik S. Reinert, How Rich Countries Got Rich … and Why Poor Countries Stay

                          Poor, London, 2007

Fekadu Bekele, African Predicaments and the Method of Solving them Effectively, Berlin, 2016

Greenfeld Liah, The Spirit of Capitalism: Nationalism and Economic Growth, London, 2001

Jiri Kosta, Jan Meyer, People`s Republic of China: Economic Development and Planning

                           System, Frankfurt am Main & Köln, 1976

Naomi Klein, The Shock Doctrine,  Great Britain, 2007

Paul Mason, Post Capitalism: A Guide to Our Future,  UK, 2015

Samir Amin, Accumulation on a World Scale: A Critique of the Theory of Underdevelopment,

New York & Lonon, 1974

Tom Burgis, The Looting Machine: Warlords, Tycoons, Smugglers, and Systematic Theft of

of African Wealth, UK, 2015

Ulrike Herrman, The Victory of Capitalism, München/Berlin, 2016