[gtranslate]

ኢትዮጵያና የቴክኖሎጂ ዕድገት ፈለግ !

በአቶ ታደሰ ንጋቱ የማቴሪያል ሳይንቲስት ባለሙያ፣  በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም የተጻፈ ባለ 337 ገጾች መጽሀፍ።

                                      ትችት፣ በዶ/ር ፈቃዱ በቀለ የስልጣኔ ተመራማሪ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለሙያና ለሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ታጋይ !                                               

ነሐሴ 20.08.2019

አቶ ታደሰ ንጋቱ በመጽሀፉ የመጀመሪያው ሽፋን ላይ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለአቆዩዋት የቴኮኖሎጂ ባለሙያዎች ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ለማመስገንና ለማስታወስ መጽሀፉን ለመጻፍ እንደተነሳሳ በዚህ መልክ ያስቀምጠዋል። ብረትን በእሳት፣ ሸክላን በውሃ፣ መሬትን በማረሻ፣ እንጨትን በስለት፣ ጥጥን በማዳወሪያ፣ ሙዚቃን በማሲንቆ፣ እየገሩ ነባራዊና ስነ-ልቦናዊ የህይወት ቁሳት በማምረት አገራችንን እንደ አገር ያቆዩልንን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎቻችንን ለመዘከር „  የተጻፈ መጽሀፍ መሆኑን ይነግረናል። መጽሀፋ በ20 ምዕራፎች የተከፈለና በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ ደራሲው የሰው ልጅ አሳቢና ተንቀሳቃሽ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ቀስ በቀስ፣ በማየት፣ በልምድና በሙከራ እንዲሁም ከስህተቱ በመማር እንዴት ወደተወሳሰበ የህብረተሰብ ዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደቻለ ነው የሚያስተምረን።

ደራሲው በመንደርደሪያው ላይ ለማሳየት እንደሚሞክረው፣ የሰው ልጅ ህይወትና ቲክኖሎጂ የተሳሰሩ ሲሆኑ፣ የሰው ልጅ ማንነትና የኑሮ ትርጉም ሊገለጽ የሚችለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ  እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። የሰው ልጅ ቀስ በቀስ ቴኮኖሎጂን በማፍለቅና በማዳበር የምርትን ዕድገት ማፋጠኑ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱን ከበሽታ ለመከላከልም ሆነ፣ አንድ በሽታ ከያዘው በኋላ ደግሞ ለመዳን የሚችለውና፣  ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚጓዘው በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው።  የባቡር ቴክኖሎጂ፣ የአውሮፕላን ስራና በአየር ላይ በመብረር ሰውን በብዙ ሺሆች የሚቆጠር ኪሎሜትር አጉዞ የተፈለገው ቦታ ማድረስ፣ የመርከብ ስራና ሰውንና ዕቃን እንደዚሁ ራቅ ያሉ ቦታዎች ማመላለስ፣ እንዲሁም በዛሬው ዓለም በስልክና እንዲያም ሲል በኢንተርኔት አማካይነት ወሬንና ኢንፎርሜሽኖችን ፊት ለፊት ሳይተያዩ መለዋወጥና የሃሳብ ተካፋይ መሆን፣ እነዚህ ሁሉ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ውጤቶች እንደሆኑ ከመጽሀፉ መረዳት ይቻላል።

ደራሲው ስለቴክኖሎጂ ምንነት ሲገልጽ በዚህ መልክ ያሰፍረዋል። ቴክኖሎጂ በአንድ በኩል እንደቁሳቁስ የሚይታይ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ምርትን ለማምረት፣ ዕቃንና ሰውን የምናቀሳቅስበትና እንዲሁም ኢንፎርሚሽን የምንለዋወጥበት በዐይን የሚታይና በእጅም የሚዳሰስ ነው።   በሁለተኛ ደረጃ ቴክኖሎጂ ጥበባዊም እንደሆነ ምሁሩ በደንብ ያስረዳናል።ይህም ማለት በቴክኖሎጂ አማካይነት ማንኛቸውንም ነገሮች ማለትም የህንጻ ስራን፣ የመብራት ኃይልን፣ የኢንጂነሪግንና ሌሎች ቴክኒካዊ ነገሮችን ሁሉ እንድናጠናበትና እንድንመረምርበት ያገለግለናል።  ስለሆነም ቴክኖሎጂ ሚዛናዊ ግምትን ለመውሰድ፣ ምርምርን ከሙከራና ከስህተት ጋር በማገናዘብ ወደ ተፈላጊው ውጤት እንድንደርስ የሚረዳን ልዩ ዐይነት ጥበባዊ ኃይል ነው። በመሆኑም ቴክኖሎጂ የአሰራር ዕቅድን ቅደም ተከተል በሚገባ ማጤን የሚያስፈልግ እንደመሆኑ መጠን አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ከተፈለገ  የግዴታ የቅደም ተከተልን ህግ ማጥናት ያስፈልጋል። አንድ ቴክኖሎጂ ከጥቅሙ ባሻገር ጉዳትም ለማድረስ የሚችል እንደመሆኑ መጠን የአንድን ቴክኖሎጂ አፈጣጠርና ዕድገት ከሁሉም አቅጣጫ ማጥናት ጉዳትን ለመቀነስ እንደዚሁ ከፍተኛ ምርምር እንደሚያስፈልግ ያሳያል። በተጨማሪም ቴክኖሎጂ የህይወታችን አንዱ አካል እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው እንክብካቤ ያስፈልገዋል።፡ በሌላ አነጋገር፣ ቴክኖሎጂ ህይወት የሌለው ቢመስልም ልዩ ልዩ ነገሮችን በጥልቀት ማየት የምንችለውና የምንመረምረው እንዲሁም ልዩ ውጤት ላይ የምንደረሰው ቴክኖሎጂ ህይወት ያለው ነገር መሆኑን የተረዳን እንደሆን ብቻና በየጊዜውም ተሃድሶ ወይም ጥገናና መሻሻል የሚያስፈልገው መሆኑን የተረዳን ብቻ ነው።   በሶስተኛ ደረጃ ቴክኖሎጂ  የተግባር መግለጫ እንደሆነ ደራሲው ያስተምረናል። በእሱ አገላለጽ  እውቀትን ከራእይ ጋር አዋህዶ ወደ ጠቃሚ ቁሳቁስነት መቀየር የሚቻለው በተግባር(በስራ) ነው።“  በማለት፣ በተለይም በአሁኑ ዘመን አንድን ለጥቅም የሚውል ቴክኖሎጂ ለማፍለቅ የግዴታ የምርምር ስራን፣ ፈጠራን፣ ቅየሳን፣ ዲዛይንን፣ የማነጽ ስራን፣ የማምረትና ተግባራዊ ማድረግም የተያያዙ መሆናቸውን  ደራሲው ያትታል። ይህም ማለት በአለንበት ዘመን እንደጥንቱ ዘመን በዘለማድ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ ምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራና፣ ቀስ በቀስም አስፈላጊውን የዕድገት ደረጃዎች አልፎ ተግባራዊ መሆን የግዴታ የተያያዙ መሆናቸው ወንድማችን ቁልጭ አድርጎ ያስረዳናል።

በአራተኛ ደራጃ፣ ስለሆነም ይላል የማቲሪያል ሳይንቲስት ተመራማሪውና፣ በዚህ ሙያ ከስላሳ ዐመት በላይ ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊው ምሁር፣ ፍላጎታችንን፣ ርዕያችንና ህልማችንን ዕውን በማድረግ ሰው መሆናችንን ማረጋገጥ የምንችለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው።  ቴክኖሎጂ ከላይ ዱብ የሚል ሳይሆን ከጭንቅላት የሚፈልቅና ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በብዙ ሰዎች ተሳትፎ ዕውን የሚሆን የሰውን ልጅ ኑሮ የሚያቃልልና ሊታለፍ የማይችለው የስልጣኔና የአንድ ህብረተሰብ ዋናው የዕድገት ቁልፍና መለኪያ እንደሆነ ውድ ወንድማችን ያስተምረናል።

ከዚህ በመነሳት አቶ ታደሰ ንጋቱ የሰው ልጅ የአለፈባቸውን የቴክኖሎጂ የዕድገት ጉዞዎች ደረጃ በደረጃ በዝርዝር ያስረዳናል። እንደሚታወቀውና በምሁሩም ዕምነት በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ በሶስት የቴክኖሎጂ ዕድገት ውስጥ እንዳለፈና ዛሬ በመጨረሻው በሶስተኛው የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያስቀምጣል። እነሱም፣ 1ኛ) ጥንታዊ የዲንጋይ ዘመን፣ 2ኛ) አዲሱ የዲንጋይ ዘመንና፣ 3ኛ) የስልጣኔ ዘመን በመባል እንደሚገለጹና፣ የሰው ልጅም በእነዚህ የዕድገት ደረጃዎች እንዳለፈና እንደሚገኝም መረዳት ይቻላል።

በዚህ መሰረት ማንኛውም ህብረተሰብ ውስጣዊ ኃይል ያለው እንደመሆኑ መጠን እዚያው ባለበት ረግቶ የሚኖር ሳይሆን፣ የሚንቀሳቀስ፣ ከአንድ  ትንሽ ደረጃ በመነሳት፣ እያደገና እየተወሳሰበ በመሄድ የሚለወጥና ከፍተኛ የሆነ በብዙ መልኮች ወይም ገጽታዎች የሚገለጽ ማህበረሰብ መመስረት እንደሚችል ደራሲው በአጠቃላይ ሲታይ ስለሰው ልጅ ዕድገት ያስረዳናል። ይህም ማለት፣ ከእንሳሳ በስተቀር ማንኛው እንደ ማሀበረሰብ ወይም እንደ ህብረተሰብ የሚኖር የሰው ልጅ የግዴታ በመጥፎም ሆነ በጥሩ ነገር እንደየሁኔታው ሊለዋወጥ ወይም ሊቀየር እንደሚችል እንማራለን። ከዚህ በመነሳት ነው ከላይ የተቀመጠው ሶስት የሰው ልጅ የዕድገት ደረጃዎች ሊገለጹ የሚችሉትና ግንዛቤ ውስጥ የሚገቡት።

በደራሲው አቀራረብና በሌሎችም የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ዕምነት ሁሉቱ የዲንጋይ ዘመኖች፣ ወይም የሰው ልጅ በዲንጋይ እየተጋዘ ኑሮውን ለማሸነፍ የቻለበት ዘመን ወደ ሶስት ሚሊዮን ዐመታት እንደሚያስቆጥር ነው። ዲንጋይን፣ እንጨትንና አጥንትን ወደ መቅረጽና  እንዲሁም ሀረግን በመስራት ማንነቱን ማረጋገጥ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውስጥ በሚከሰቱ የተፈጥሮ ቁጣዎች ሰለባ እንደነበረና ቀስ በቀስም ራሱን በማግኘት ዲንጋይን በማሾል፣ እንጨትንና አጥንትን በመቅረጽና ደጋን በመስራት ራሱን ከአደጋ ለመከላከልና በተፈጥሮ ውስጥም የሚገኙ እንስሳዎችን እያደነ መብላትና መኖር የቻለው በእዚህ ዐይነቱ  ራሱ በፈጠራቸው ቴክኖሎጂዎች እየታገዘ መሆኑን እንማራለን።

በአጋጣሚ እሳት ከተገኘ በኋላ የሰው ልጅ ህይወት ከፍተኛ ምጥቀትን ማግኘት ይጀምራል። እሳት ምግብን ለመቀቀያ፣ ለመብራትና ራስን ከአደጋ ለመከላከል፣ ለሰውነት ሙቀት መለገሺያ፣ ለብረት ማቅለጪያና መሳሪያዎችን ለመቅረጽና ለመስሪያ የሚያገልግል ልዩ ኃይል ነው። በእሳትና የኋላ ኋላ ደግሞ ኃይል(Energy)በሚባለው ልዩ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ልጅ የፈጠራ ሀብት አማካይነት ብቻ ነው የሰው ልጅ ከእንስሳ ባህርዩ ለመላቀቅና ቴክኖሎጂዎችን ቅርጽ በመስጠት፣ ሸክላን በማቃጠልና ቤት በመስራት ቀስ በቀስ መንደሮችንና ከተማዎችን በመገንባት ተሰባስቦ ለመኖር የቻለው። ይህም የሚያመለክተው በአንዳች ምክንያት ካልተዘጋ በስተቀር የሰው ልጅ ጭንቅላት ተንቀሳቃሽ የሆነና በማሰብ ኃይሉም ልዩ ልዩ ነገሮችን በመፍጠር ወደ ተወሳሰበና በስራ-ክፍፍል ወደሚገለጽ ማህበረሰብ እንደሚያመራ ነው።

በዚህም መሰረት የሰው ልጅ ከመጀመሪያው የዲንጋይ ዘመን ወደ አዲሱ በመሸጋገር ቀስ በቀስም የእርሻ ቴክኖሎጂን  ያዳብራል።  ቀደም ብሎ በአደንና ፍራፍሬን በመልቀም ይተዳደር የነበረው የሰው ልጅ  አሁን በእርሻ ቴክኖሎጂ አማካይነት መዝራትንና ማብቀልን፣ እንዲሁም ፍሬውን ለቅሞ መመገብን ይማራል። ይህ ዐይነቱ አዲስ ቴክኖሎጂ ደግሞ የበለጠ ምርምርን የሚጠይቅ ሲሆን፣ የሰው ልጅም በመጀመሪያ ደረጃ በማየትና በኢንቲዩሽን ለምግብ የሚያገለግሉትን በመምረጥና  በማባዛት እየዘራ ምርትን በማሳደግ ወደተሻለ የህብረተሰብ ዕድገት ደረጃ ይደርሳል። ከዚህ በመቀጠልም ለመለማመድ የሚችሉ ከብቶችን በማቅረብና በማራባት የስጋና የወተት፣ የአይብና የቺዝ ፍላጎቶቹን ያሟላል።

ደራሲው እንደሚያስረዳን በዚህ ዐይነቱ የአዕምሮ እንቅስቃሴና የማሰብ ኃይል አማካይነት ቴክኖሎጂዎች መዳበራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ መንደሮችንና ከተማዎችን በመመስረት ወደ ማህብረሰብና ወደ መንግስት ምስረታ ለማምራት እንደቻለና፣ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አመለካከታቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ ለማድረግ የቻሉበትን  ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። ይህም ማለት ስርዓት ያለው ማህበረሰብና መንግስት መመስረት የሰው ልጅ ባህላዊና ታሪካዊ ግዴታዎች እንደሆኑ እንማራለን። በዚህም አማካይነት፣ የሰው ልጅ ከዲንጋይ ቴክኖሎጂ ወደ ብረታብረት ቴክኖሎጂ፣  ወደ ህንጻ ቴክኖሎጂና  የጽሁፍ ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ወደ ሂሳብና ወደ ጊዜ መቁጠሪያ ቴክኖሎጂ በመሸጋገር ተፈጥሮን ወደ መቆጣጠር እንዳመራ ከደራሲው መማር እንችላለን። ይህ ዐይነቱ የቴክኖሎጂ ምጥቅት ቀስ በቀስ ወደ ተወሳሰበና አንድ ወጥ ወዳልሆነ ማሀበረሰብ ለመጓዝ እንዳስቻለ መረዳት ይቻላል።

በዚህ አማካይነት ደግሞ የግዴታ የተመሰረቱ ማህበረሰቦች እንደቀድሞው በእኩልነት ደረጃ ላይ የሚተያዩ ግለሰቦች ያሉበት ሳይሆን ገዢና ተገዢ፣ በዝባዥና ተበዝባዥ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ የህብረተሰብ ክፍሎች የግዴታ ከህብረተሰብ ዕድገት ጋር የተከሰቱ ሁኔታዎች እንደሆኑ እንመለከታለን። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ሂደት አንደኛውና ኃይል ያገኘው የህብረተሰብ ክፍል የተፈጥሮን ሀብት እንዲቆጣጠር ሲያስችለው፣ በዚያው መጠንም ህብረተሰብአዊ ዕድገት ሚዛናዊ ከመሆን ይልቅ ዕድገቱ አንደኛውን የሚጠቅም ብቻ እየሆነ ይመጣል። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ዕድገት ቀስ በቀስ አስተሳሰብንና ዕድገትን ወደሚያፍን፣ እንዲያም ሲል የሳይንስን ግኝት ወደሚቀናቀን ፊዩዳላዊ ስርዓት ያመራል። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ዕድገት በአገራችንና በአውሮፓ ምድር የተከሰተና እንደተፈጥሮአዊ የህብረተሰብ ስርዓት የተወሰደ ሲሆን፣ በአውሮፓ ምድር ሰፋ ባለና በማያቋርጥ ምሁራዊ እንቅስቃሴና የመደብ ትግል ሲገረሰስ፣ በአገራችን ምድር ግን ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ በመቆየት ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት እንዳይኖር እንቅፋት ሆኗል።

በደራሲውና በሌሎችም ምሁራን ምርምር መሰረት የሰው ልጅ ከፍተኛ ዕድገትን መቀዳጀትና ቴክኖሎጂዎችን ማዳበር የቻለው ባለፉት አምስትና ሁለት ሺህ ዐመታት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት ከተካሄደና፣ ከዚያ በኋላ ባለፉት ሁለት መቶ ዐመታት ሳይንሳዊ ምርምር ለቴክኖሎጂ ማግኝያ ዋናው የቁልፍ ዘዴ መሆኑ ከተደረሰበት ወዲህ የሰው ልጅ ከፍተኛ እርምጃን እንዳደረገ መረዳት ይቻላል።  ከዚያ በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች በተገለጸላቸው ምሁራን አማካይነት የተገኙት ፍልስፍናዎችና የምርምር ዘዴዎች ለዘመኑ ስልጣኔ ዋናው መነሾዎች እንደሆኑ ደራሲው በዝርዝር ያስረዳል፣ በሜሶፖታሚያ፣ በአባይ በተለይም በግብጽ አካባቢና፣ ይህ ስልጣኔ ቀስ በቀስም ወደ ግሪክ መምጣቱና የተፈጥሮ ፈላስፋዎች በመባል የሚታወቁት መመራመሪያ ዘዴ መሆን ከጀመረ ወዲህ የሰው ልጅ በማያጠራጥር ሁኔታ የስልጣኔውን ቁልፍ ማግኘት እንደቻለ እንማራለን። ስለሆነም የግሪክ የመጀመሪያዎቹ የተፈጠሮ ፈላስፋዎች በመባል የሚታወቁት የተፈጥሮን ልዩ ልዩ ነገሮች፣ ማለትም ነፋስን፣ ውሃን፣ መሬትንና እሳትን የማንኛውም ነገሮች መነሻ መሆናቸውን ከገለጹ ወዲህ የስልጣኔው ቁልፍ እንደተገኘ ይታወቃል። በኋላም የተነሱት ፈላስፋዎች ይህንን መሰረት በማድረግ ወደ ከፍተኛ ምርምር በማምራት የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ ማንኛውንም ነገር ማፍለቅና ራሱን ማሻሻል እንደሚችል ይደርሱበታል። ይህ የምርምር ዘዴ ለግሪኩ የመጀመሪያውን ስልጣኔ በር የከፈተ ሲሆን ማቲማቲክስ፣ ፊዚክስንና አስትሮኖሚን፣ እንዲሁም ባዮሎጂ የምርምር ዘዴዎች በመሆን ለእነ አርቺመዲስ የመካኒክስ ምርምርና ፈጠራ ስራ መንገዱን እንዳሳዩት መገንዘብ እንችላለን።  በዚህም መሰረት የነፋስና የውሃ ቴክኖሎጂዎች በመዳበር የሰው ልጅ ቴክኖሎጂዎችን ለማንቀሳቀስ የሚችልበትን የኃይል ምስጢር እንዳገኘ እንማራለን።

የግሪክ ስልጣኔም በሮማውያን ከተነጠቀና የተወሰነው ከወደመ በኋላ ሮማውያን ይበልጥ ያደሉት የመሳሪያ ቲክኒክን በማዳበር፣ የካናል ሲስተምን በመስራት፣ ከተማዎችን በልዩ መልክ በማስፋፋት ለአዲሱ የስልጣኔ ዘመን በር ለመክፈት እንደቻሉ እንገነዘባለን። በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የሮማውያን ስልጣኔ ከወደመ በኋላ የጨለማው ዘመን በመተካት ሳይንሳዊ ግኝቶችና የቴክኖሎጂ ምርምሮች በከፍተኛ ደረጃ  ወደ ኋላ የተጓተቱበትን ዘመን ደራሲው ያስቀምጣል። ይሁንና ግን ይህ ዕይነቱ የጨለማ ዘመን የግሪኩን ስልጣኔ መልሶ ማግኘት በመባል በሚታወቀው በሬናሳንስ አማካይነት፣ ቀጥሎም በሪፎርሜሽንና በኢንላይተንሜንት አማካይነት የጨለማው ዘመን እንደተወተገደና የሰው ልጅም በቴክኖሎጂ አማካይነት ከማንኛውም የተፈጥሮ ጭነት መላቀቅ የሚችልበት መንገድ የተከፈተለት ለመሆኑ ከመጽሀፉ መረዳት ይቻላል። በሬናሳንስ ዘመን የእነጋሊሌዮ ምርምር፣ የሬኒ ዴካር ሳይንሳዊ ግኝት፣ ቀጥሎም የኒውተን የግራቪቴሽንና የአስትሮኖሚ ምርምሮች፣ በኒውተንና በላይብኒዝ አማካይነት ካልኩለስ በመባል የሚታወቀው የቲክኖሎጂ ቁልፍ የሆነው የማቲማቲክስ አንድ አካል ከተገኘ በኋላ ሳይሳዊ ምርምርና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገትና መሻሻል የተያያዙ መሆናቸውን የዚህ መጽሀፍ ደራሲ በዝርዝርና በግሩም መልክ ያስረዳናል። በእሱ እምነትም አንድ ቦታ ላይ የተጀመረ ምርምርና ቲክኖሎጂያዊ ዕድገት ተከታታይነት ሊኖራቸው የቻለው በማያቋርጠው የጥቂት ሰዎች ያለመስልቸት ጥረትና ትግል እንዲሁም ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደሆነ ከመጽሀፉም ሆነ ከልዩ ምርምሮች መማር ይቻላል። ይህም ማለት በአውሮፓ ምሁር ዘንድ እንደባህል የተወሰደው  የቴክኖሎጂን ግኝት እንደምስጢር መያዝና ማዳፈን ሳይሆን፣ ተከታዩ ትውልድ እንዲያዳብረውና ለሰው ልጅ መጠቀሚያ እንዲያደርገው መንገዱን አሳይቶ ማለፍ ነው። በዚህም መሰረት ተከታታዩ ትውልድ ሳይሰለችና ግዴታው መሆኑን በመረዳትና ኃላፊነቱን በመወጣት ከራሱ ማህበረሰብ አልፎ ለዓለምም ህዝብ መጠቀሚያ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማዳበርና ማሻሻል እንደቻለ መገንዘብ እንችላለን።     ደራሲው የማቴሪያል ቴክኖሎጂ ተመራማሪ እንደመሆኑ መጠን ዛሬ የምንጠቀምባቸው በቴክኖሎጂ አማካይነት የተገኙ የተፈጥሮ ውጤቶችና፣ እንዲሁም አንደኛውን ከሌላው ጋር በማቀናጀትና በማዋሃድ ልዩ ዐይነት ባህርይ ያለውና ጠቀሜታ የሚሰጥ ምርት ወይም ቴክኖሎጂ ማግኘት የግዴታ ከፍተኛ ምርምርን እንደሚጠይቅ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ቴክኖሎጂ የተገኘውና ዛሬም የዳበረው በመሰረቱ ቲክኖሎጂን ለማግኘትና የተወሰኑ ሰዎችን ለመቆጣጠሪያ  ሳይሆን የሰውን ልጅ ኑሮ ለማቃለል ብቻ ነው። ደራሲው እንደሚያስተምረን፣ በተለይም በኒዎ-ክላሲካልና በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰለጠኑ ኢኮኖሚስቶችን አስተሳሰብና ትረካ ፉርሽ በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገት ከቴክኖሎጂ ውጭ በፍጹም ሊታሰብ እንደማይችል ነው። ከዚህ ስንነሳ በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለና ርስ በርሱ የተሳሰረ በብዙ መልኮች የሚገለጽ የስራ ክፍፍል መኖር፣ የመንደሮችና የከተማዎች ዕድገት፣ የእነዚህ በተለያዩ የመገናኛ መስመሮችና መመላለሻዎች መያያዝ፣ ህንፃዎች ውብ በሆነ መልክ መሰራትና ህብረተሰብአዊ ባህርይ መያዝ እነዚህ ሁሉ ከቴክኖሎጂ ዕድገትና እንዲያም ሲል ሰፋ ካለ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚያያዙ ናቸው። በመቀጠልም አንድ አገር ልታድግ የምትችለው አንድ ህዝብ ራሱን በራሱ ማግኘት ሲችልና ለፈጠራ የሚያመቹ ሁኔታዎች ሲዘጋጁለት ብቻ ነው። ከዚህ ስነነሳ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ህዝባዊ ባህርይ ያለው መንግስታዊ አወቃቀርና እንዲሁም ግለሰብአዊ ነፃነት የግዴታ ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመቹ ናቸው። በተጨማሪም ለቴክኖሎጂና በዚህ ላይ ለሚመሰረተው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት  ህብረተሰብአዊ ሰላምና መፈቃቀር የግዴታ አስፈላጊዎች ናቸው። የአገር ወዳድነት ስሜት በሌለበትና አስረሽ ምችው በሰፈነበትና የዘረፋ ኢኮኖሚ በሚካሄድበት አገር፣ አንድ አገር የቴክኖሎጂ ምጥቀትን በማግኘት ራሷን ልታስከብር አትችልም። በመሆኑም አንድ ህዝብና አንድ አገር የሚከበሩት ከውስጥ በሚያሳዩት በማያቋርጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዕድገት አማካይነት ከፍተኛ ጥረት ብቻ ነው። ይህ በራሱ ደግሞ በተለይም በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ  የሞራል ጥንካሬን ይጠይቃል።  የስልጣኔን ምንነት የተረዳ፣ ራሱን ከህዝቡና ከአገሩ ጋር ያገናኘና በጥቅም በመደለል የአገሩን ምስጢር ለውጭ ኃይል አሳልፎ የማይሰጥ ምሁራዊ ኃይል ባለበት አገር ብቻ የቴክኖሎጂ ምጥቀት መታየቱ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝቡም ኑሮ ደረጃ በደረጃ እየተሻሻለ ይመጣል። ይህ ሁኔታ በሌለበት አገር ደግሞ ዘለዓለማዊ ድህነትና ውርደት የአንድ ህዝብ መገለጫዎች ይሆናሉ።

ደራሲው የቴክኖሎጂን ለችግር መፍቻ ቁልፍነት በማሳሰብ፣ በተለይም ለብዙ ሺህና መቶዎች ዐመታት አነሰም በዛም ለቴክኖሎጂ ዕድገት የተደረገውን ትግል አለመዘንጋትና የነበሩትንና ያሉትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ያሳስባል። ከዚህም በመነሳት በሌላ ወገን ደግሞ ካለማወቅ የተነሳ ቴክኖሎጂ አፍላቂዎችን በማንቋሸሽና ቡዳ እስከማለት ድረስ በማግለል በወገኖቻችን ላይ ይደርስ የነበረውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመኮነን፣ ከዚህ ዐይነቱ አላስፈላጊና አላዋቂ ድርጊት በመታገድ ለቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ልዩ ቦታና ክብር መስጠት እንደሚያስፈልግ በጥብቅ ያስስባል። በተለይም አዲሱ ትውልድ ቴክኖሎጂ ለአገር ዕድገትና ለችግር መፍቻ ዋናው ቁልፍ መሆኑን በማሳሰብ፣ በአንድ አገር ውስጥ መረጋጋርትና ሰላም ሊፈጠር የሚችለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ሰፋ ያለ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሲፈጠርና በዐይነት እየተሻሻለ የመጣ እንደሆን ብቻ ነው።

በዚህ ተቺ ዕምነትና አመለካከት በኢትዮጵያ ምድር መሰረታዊ የሆነ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የመንግስት ጥያቄና ሚና እንዲሁም ፖለቲካ የሚባለው ትልቁ ጽንሰ-ሃሳብ መስመር መያዝ አለባቸው። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ከሳይንስ አንፃር መፈታት አለባቸው። የመንግስትን መኪና የሚጨብጡ ሰዎች በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑና ሁለ-ገብ ዕውቀት ያላቸውና፣ ዋና ዓላማቸውም ህገ-መንግስትን ማክበርና አገርን ማበልጸግ መሆን አለበት። ፖለቲካ ከዕውቀት ጋር ካልተያያዘና የአንድ ህዝብም ምንነት በሚገባ ግንዛቤ ውስጥ እስካልተገባ ድረስ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ ዕድገት፣ እንዲያም ሲል ረሃብንና ድህነትን ስለማሰወገድ ጉዳይ በፍጹም ማውራት አይቻልም። በዚህ ላይ ደግሞ በስልጣን ላይ የሚወጡና፥ ምሁሩ በአጠቃላይ አገርና ስልጣኔ በሚለው ላይ የሚያስማማ በሳይንስ የተፈተነ ሃሳብ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት የርስ በርስ ሽኩቻንና በሳይንስ ላይ ያለተመሰረተን የሃሳብ መናቆርን አይሹምና። ከዚህ በሻገር በኢትዮጵያ ምድር መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያፈልጋል። በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የመንፈስ ተሃድሶ እንደሚያስፈልግ ነው። እንደኛው ባለው ፣ አሁንም ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ በሰፈነበትና ይሉኝታ በበዛበት አገር ስለሳይንስና ስለቴክኖልጂ ዕድገት በፍጹም ማውራት አይቻልም።

የአቶ ታደሰ ንጋቱ መጽሀፍ ከረጅም ጊዜ ምርምር በኋላ በከፍተኛ የአገር ወዳድነት ስሜት የተጻፈ መጽሀፍ ነው። መጽሀፉን መስመር በመስመርና ገጽ በገጽ ላነበበ ውድ ወንድማችን ጠለቅ ያለ የህብረተሰብ ዕድገት ግንዛቤና እንዲሁም የዓለምን የስልጣኔ ታሪክ በደንብ ያነበበና የተረዳ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ለቴክኖሎጂ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን በጥብቅ የሚያውቅና ከሰላሳ ዐመት በላይ በሙያው የሰራና አሁንም እየሰራ ያለው ታላቅ ሰው ነው። በዚህ ዐይነት ታሪካዊ አስተዋፀዖውም ልናመሰግነው ይገባናል። እኛም በበኩላችን በተማርንበትና በሰለጠንበት የሙያ መስክ ልክ እንደሱ በአማርኛ እየጻፍን መጽሀፍ ብናሳትምና ለወጣቱ ትውልድ መማሪያ ብናቀርብ የታሪክን ኃላፊነት ተወጣን ማለት ነው። መጽሀፉ መነበብ ያለበት ስለሆነ ማንኛው ለአገሩ ዕድገት የሚቆረቆርና አስተዋፅዖ ለማድረግ የሚፈልግ ይህንን መጽሀፍ ገዝቶ ማንበብ ይኖርበታል።

                                        fekadubekele@gmx.de