[gtranslate]

ህወሃትን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ የታቀደ ስብሰባ ወይስ በአብሮ የመኖር ስም አንድን አገዛዝ ብቻ ተጠያቂ ለማድረግ የታቀደ የውይይት መድረክ!!

                                                                                                                                                                                                                   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                                                                                                                                                             (ሰኔ 23 2017)  June 30, 2025

እ.አ.አ በሰኔ 7፣ 2025 ዓ.ም “የርዕዮት ሚዲያ” ባለቤት የሆነው ቴዎድሮስ ፀጋዬና፣ “የአብሮነት ኢትዮጵያ” አሰባሳቢ መሪ ነኝ የሚለው ልደቱ  አያሌው “ታላቅ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ” በሚል፣ ይሁንና ዋናው መሰረተ-ሃሳብ” ጦርነት ይቁም፣ ግፋዊ አገዛዝ ያቁም፣ ዘላቂ ሰላም ይስፈን” በሚሉ ርዕሶች ስር “ይታወቃሉ የሚባሉ ግለሰቦች” በተጋበዙበት የኦን-ላይን ዝግጅት ላይ ውይይት ተካዷሂል። ከተጋበዙትም ውስጥ ጀዋር መሀመድ፣ በአንድ ወቅት የፖለቲካውን መድረክ በመቆጣጠርርና ቄሮ የሚባሉ ወጣቶችን በማሰባሰብ፣ በተለይም በናዝሬትና በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሄረሰብ  ተወላጆች ላይ እንዲነሱ ያደረገና፣ ብዙ የአማራ ወገኖቻችን እንዲገደሉ ምክንያት የሆነ፣ አንድም ቀን ሳይሰራ የመቶ ሚሊዮን ትልቅ ቪላ ቤት ባለቤትና የናጠጠ ቱጃር የሆነ፣ ከዚህም በላይ አዲስ አበባ የሚኖርበት መንደር ቪላ ቤቱ ውስጥ እያለ በምሽቱ ሰዎች ቤቴን በመክበብ ሊገሉኝ ነው ያለና፣ በውሸትም ብዙ ሰዎች ያስጨረሰ፣ ወይዘሮ ምስጢረስላሴ ታምራት የኢህእፓ ዋና ፀሀፊ ነኝ የምትል ወጣት ሴት፣ በትክክል የኢህአፓን የትግል ታሪክና አስተዋፅዖ ወይም ወንጀል ታውቅ ወይም አታወቅ እንደሆነ የምታውቅ የማትመስል፣  አሉላ ሰለሞን ኗሪነቱ በአሜሪካን አገር የሆነና፣ ለረጅም ዐመታት የወያኔ ካድሬ በመሆን በአሜሪካን ምድር የትግራይን ወጣቶች በማሰባሰብ የወያኔ አገዛዝ የበላይነቱን ይዞ እንዲቆይ የታገለና፣ ወያኔም ከስልጣን ላይ ከተባረረ በኋላ በጠቅላላው የትግራይ ብሄረሰብ ላይ ጦርነት እንደሚካሄድ አድርጎ የውሸት ወሬ ሲያናፍስ የነበርና ምንም ሳይሰራ የናጠጠ ሀብታም የሆነ፣ ገዱ አንዳርጋቸው የቀድሞው የብአዴን የአመራር አባል የነበረና በአማራ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበረውና፣ በአማራ ክልል ውስጥ በአመራር ላይ በነበረበት ጊዜያት አማራውን የሚጥቅምና ከድህነት የሚያላቅቀው ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ ያላደረገ፣ ኋላ ላይ በአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ደመቀ መኮንን በመተካት ለአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምኒስተር በመሆን ያገለገለ፣ አሁን ኗሪነቱ በአሜሪካን ምድር የሆነ፣ ፕሮፌሰር ነኝ የሚለውና የኦሮሞ ተወላጅ ነኝ በማለትና “ኦሮሞዎች ከሴሞች የተለየ የኩሽ ስልጣኔ የነበራቸውና፣ በአፈጣጠራቸውም ከውሃ ውስጥ የፈለቁ ናቸው” እያለ የሚያወራውና፣ አፄ ምኒልክን አላውቅም በማለት የሚታወቀውና፣ አቢይ አገዛዝ ስልጣንን ከህወሃት እንደተረከበ ሰሞን ኢትዮጵያ ውስጥ በመግባት የኦሮሞን የበላይነት ለማስፈን ውር ውር ሲል ከነበሩት ውስጥ አንዱ የሆነው ኢዝኪዬስ ገቢሳ፣ ስብሃት ነጋ የሚባለው አሁን ኗሪነቱ በአሜሪካን ምድር የሆነና፣ የቀድሞውና የአሁንም የውሃት ታጋይ፣ የኦርቶዶክስን ሃይማኖትና የአማራውን ብሄረሰብ በጣም የሚጠላው፣ ዘመቻም ያደርግ የነበረና ለረጅም ዓመታት የህውሃት መሪ በመሆን በበረሃ ውስጥ የታገለና በረሃ ውስጥ በነበረበትም ጊዜያት ሌላ አስተሳሰብ በነበራቸው የትግራይ ተወላጅ ታጋዮች ላይ ከግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን ካለምንም ርህራሄ የጨፈጨፈና፣ ሴቶችንም በመድፈርና ወደ ገደል ውስጥም በመውረር የሚታወቀውና፣ ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያ የዕድገት ምርምር ተቋም(Ethiopian Development Research Institute) ኃላፊ የነበረ፣ ይሁንና ምንም ዐይነት የምርምር ጥናት ያላቀረበና፣ ኢትዮጵያም በዚህ መልክ ነው ማደግ የምትችለውና፣ ህዝባችንም ከድሀነትና ከኋላ-ቀርነት ሊላቀቅ የሚችለው በማለት አንድም ጥናታዊ ጽሁፍ ያላቀረበ፣ አብዛኛውን ጊዜውን የተለያዩ የውስኪ ዐይነቶችን በመጠጣት የሚያሳልፈውና ጭንቅላቱም የደነዘዘ፣ ወያኔም በዘረጋው የዘረፋ ሰንሰለት ውስጥ በመካተት የኢትዮጵያን ሀብት የዘረፈና በአገራችንና በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመ፣ አማኑኤል ሞገስ የሚባል ግለሰብና ሌሎችም እንደ የሱፍ ያሲን የሚባለው የአፋር ብሄረሰብ ተወላጅ የሆነው በውይይት መድረኩ ላይ በኦንላይን(Online) ተሳትፈዋል። ከእነዚህ በስተቀር በአንደኛው ዋና አዘጋጅ በልደቱ አያሌው በኦንላይን የውይይት መድረክ ላይ እንዲሳተፉ ከተጋበዙት ውስጥ፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስተር ተብዬው አቢይ አህመድ፣ የህወሃት መሪ የሆነውና ኢትዮጵያን በማድማት፣ በመዝረፍና ስንትና ስንት ወንጀል በመስራት የሚታወቀው ደብረ-ፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ የሳንሳዊ ወያኔ መሪ ነኝ የሚባለው አሉላ ኃይሉ፣ ታዬ ደንደዓና፣ ከፋኖ ውስጥ አንደኛው ክንፍ  የሆነው እስክንድር ነጋ ብቻ ተጋብዘው በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ አልፈለጉም፣ ወይም ደግሞ አልቻሉም። ከፋኖ አመራርውስጥም ለምን እስክንድር ነጋ ብቻ እንደተጋበዘ ልደቱ አያሌው አላባራም። ይሁንና በዚህ ዐይነቱ አካሄዱ ከፋፋይ እንደሆነ ነው ለማረጋገጥ የቻለው። በፋኖዎች ውስጥ ያለውን ክፍፍል በመጠቀም ክፍፍሉ ጥልቀት እንዲኖረው ያሰበው ሴራ ነው ማለት ይቻላል። የዝግጅቱ ዋና ኃላፊ የሆነው ልደቱ አያሌው ለምን አቢይ አህመድንና ደብረጽዮን ገብረሚካዔሊን እንደጋበዛቸው ምንም የሰጠው ማብራሪያ የለም። በዝግጅቱ ውስጥ የተሳተፉትን ራሱን ልደቱ አያሌውን፣ ጀዋር መሀመደንና ደጉ አንዳርጋቸውን ለጊዜው ብንተዋቸውም አቢይ አህመድና ደብረጽዮን ገብረሚካዔል ለምን እንደተጋበዙና ምንስ ማብራሪያ እንደሚሰጡ በመታሰብ እንደሆነ ልደቱ አያሌው የተናገረው ነገር የለም። ሁለቱም ወንጀለኞች መሆናቸው እየታወቀና፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እዚህ ዐይነቱ የውድቀት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካደረጉት ሰዎች ውስጥ ሁለቱም በዋና ግንባርነት የሚታወቁ መሆናቸውና፣ በአገር ክህደት፣ በዘረፋ፣ ህዝብን በመከፋፈልና ርስ በርስ እንዲበላላ በማድረግና፣ ራሳቸውም ህዝብን በመጨፍጨፍ የሚታወቁ ሲሆንና በሰሩት ከፍተኛ ወንጀልም በህግ የሚጠየቁ ሰዎች መሆናቸው እየታወቀ ልደቱ አያሌው በምንም መለኪያ  እንደጋበዛቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ምናልባት እነሱም እንደራሱ ራሳቸው ለፈጠሩት ምስቅልቅል ሁኔታና ህዝባዊ ሰቆቃ መፈትሄ ሊሆኑ ወይም መልስ ሊሰጡ ይችላሉ ብሎ አስቦ ነው ወይ? በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከላይ የተዘረዘሩትንና አብዛኛዎቻችን የምናውቃቸውን ወንጀሎችና ክህደት ከፈጽሙ ፍቱን መፍትሄ መጠበቅ ይቻላል ወይ? እኛው ራሳችን የፈጠርነው ወንጀል ነው ብለውስ ሊያምኑ ይችላሉ ወይ? ቢያምኑስ ምንስ ነገር ከእነዚህ ሁለት ግለሰቦችና ከስብሃት ነጋ ከመሰሳሉት ጭንቅላቱን በጨው ከታጠበ ሰው መጠበቅ ይቻላል? ለማንኛውም ልደቱ አያሌው እንደነዚህ ዐይነት ወንጀለኞችን የመፍትሄው አንድ አካል ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መጋበዙ አይ የሚያደርገውን አያውቅም፣ ወይም እያወቀ አብዛኛው አዳማጭ ወይም ተመልካች ሊገባው አይችልም ብሎ  በመገመቱ ሊሆን ይችላል። በታሪክ ውስጥ ስልጣን ላይ የነበሩና ስንትና ስንት ወንጀል የፈጸሙ፣ ይቃወመናል የሚሉትን በሙሉ አይ ያሰሩ፣ በእስር ላይም እንዳሉ እንዲሰቃዩ ያስደረጉ፣ ያስገደሉና በአጠቃላይ በአገርና በህዝብ ላይ ክህደት ወይም ወንጀል የፈጸሙ እንደመፍትሄ አቅራቢ፣ ወይም አማራጭ ሃሳብ አፍላቂ ሆነው የተጋበዙብት ጊዜ የለም።  በዚህም አካሄዱ አሜሪካና ግብረ-አበሮቹ ራሳቸው የፈጠሩትን ጦርነትና ስንትና ስንት ሰውን ካስጨፈጨፉ በኋላ ለምን ተቀምጣችሁ አትነጋገሩም፣ ተስማምታችሁስ አትሰሩም ወይ እንደሚሉት ዐይነት ፌዝ ይመስላል። አሜሪካና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲሁም የአውሮፓው አንድነት ኤክስፐርት ነን የሚሉት በሙሉ ህወሃትን እስከዛሬ ድረስ አቅፈው ደግፈው የያዙት እነሱ የሚፈልጉትን ወንጀል ስለሚሰራላቸው ነበር። ልደቱ አያሌው ልክ እንደ አባቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በዚህ ዐይነቱ መንፈስን በሚሰልብና ርህራሄ በሌለው አስተሳሰብ የሰለጠነ ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር እንዲባባስና ህዝባችንም ለዝንተዓለም ከጭቆና ስርዓት እንዳይላቀቅ የማይሸርበው ተንኮል የለም።

ወደ ዋናው የውይይቱ አርዕስት “ጦርነት ይቁም፣ ዘላቂ ሰላም ይስፈን፣ ግፋዊ አገዛዝ ይቁም፣ በልደቱ አያሌው አባባል “አገዛዝ ያክትም” ወደሚሉት መሰረተ-ሃሳቦች ጋ ስንመጣ በጣም ጥቂት ካልሆኑትና ህይወታቸውንም ሰውን በመግደል፣ ከቀየው በማፈናቀል፣ ሀብቱን በመዝረፍ፣ የጥሬ-ሀብቱን በመቀራመት፣ የውጭ ኃይሎች አገልጋይ በመሆን አገራችንን የጦር አውድማ ካደረጉት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ምክር በመቀበል ባለፉት ሰላሳ አምስት ዓመታት አገራችንን ያቆረቆዘና ህዝባችንን ያደኸየ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸውን ከሚያደልቡትና፣ የብልግና ኢንዱስትሪም እንዳስፋፉትና፣ ይባስም ብለው እንዲስፋፋ ከሚያደርጉት፣ ስልጣንን ከተቆናጠጡትና ከግብረ-አበሮቹ በስተቀር ወደ 95% የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጦርነቱ እንዲቆምለት፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንለትና ጭፍጨፋም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ እንዲቆምለት ይፈልጋል፤ ለዚህም ይፀልያል። የጥያቄው አነሳስ ትክክል ቢሆንም እነዚህ ከላይ የሰፈሩትና“ውይይትም የተደረገባቸው”፣ በእኔ ዕምነት ስርዓት ባለውና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ የተካሄዱ አይደሉም፣ ለችግሮቹ በዋናነት ማን ተጠያቂ እንደሚሆንና ለምንስ እንደዚህ ዐይነት ነገሮች ሊደረጉ ቻለ፣ ይህ ዐይነቱ ወንጀለስ ከአገሪቱ ህገ-መንግስት ጋር የሚጋጭ አይደለም ወይ? ወይስ በህገ-መንግስቱ የተደገፈ ነው? ተብሎ በሚገባ ተብራርቶ አልቀረበም። የጥያቄው አነሳስና የተካሄደውም ውይይት የሚያመለክተው፣ አዘጋጆችም ሊያስምኑን እንደሚሞክሩት እንደ አጀንዳነት የቀረቡት ነጥቦች በሙሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ተግባራዊ የሆኑና፣ ለእዚህም ዋናው ተጠያቂ አቢይ አህመድና እሱ የሚመራው የብልጽግና አገዛዝ እንደሆኑ አድርጎ ብቻ ነው የቀረበው። በእርግጥም ባለፉት ሰባት ዓመታትና እስካሁንም ድረስ ለሚካሄደው አገርን የማፈራረስ፣ ሰላምን የማሳጣት፣ ማብሪያ ሊኖረው የማይችል ጦርነት ማካሄድ፣ ህዝብን መጨፍጨፍና፣ በተለይም ደግሞ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማካሄድን አስመልክቶ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮች ዋናው ተጠያቂዎች ናቸው። ስህተቱ ግን ይህ ዐይነቱ ድርጊት በአቢይ አህመድ አገዛዘ ዘመን ብቻ የተጀመረ፣ እንደሚካሄድና፣ ዋናው ተጠያቂም ራሱና አገዛዙ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብና መወያየት ትክክል አይደለም። ይህ ዐይነቱ አካሄድና ከጋባዞቹና ከታገበዙት ውስጥ አንዳንዶችን ስንመለከት ልደቱ አያሌው ህወሃትን ከደሙ-ንፁህ እንደነበር  አድርጎ ለማቅረብ ነው የሚሞክረው፤ በእግጥም አካሄዱ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። ልደቱ አያሌው በህወሃት የአገዛዝ ዘመን ተጠቃሚ የነበረና ልክ የህወሃትን አገዛዝ ይቃወም ይመስል ፓርሊያሜንቱ ውስጥ በአስመሳይነት በመቀመጥና አንዳንዴም ከእነ መለሰ ዜናውና ጋር በሃሳብ የማይስማማ አስመስሎ ሲናገር በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍልም ተደማጭነትን ለማግኘት ችሎ ነበር፤ በዚህ ዐይነት መሰሪህ ስራው ወይም ተልዕኮው እንደ ላሊበላ የመሳሰሉ ሆቴል ቤቶችን ላሊበላ ከተማ ያሰራ ነው።

የነገሮችን ሂደት በሚገባ ለመመልከትና ለመገንዘብ የግዴታ አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ህዝባችንና  አገራችን የነበሩበትን ሁኔታና፣ ህወሃትም 27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ሲገዛ ተግባራዊ ያደርግ የነበረውን ፖለቲካ-በመሰረቱ ፖለቲካ ሳይሆን ውንብድና- የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስልጣንም ላይ እንዴት እንደወጣና ማንስ ከበስተጀርባው እንደነበር ጠጋ ብለን እንመልከት። በተለይም አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የሚሰራውን መጠነ-ሰፊ ወንጀል ለመገንዘብ የምንችለው ወያኔ የጣለውን መሰረት፣ ወይም ተግባራዊ ያደርግ የነበረውን ፖለቲካ፣ በመሰረቱ ብሄረሰብን ከብሄረሰብ ጋራ ማናከስ፣ ኢትዮጵያን በጎሳ በመከፋፈል መተማመን እንዳይኖር ማድረግ፣ በዚያውም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመነሳት አገሩን እንዳይገነባ ማድረግና ብሄራዊ ስሜትም እንዳይኖረው የተተበተበው ሴራ፣ የውጭ ኃይል በመሰረቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግብረ-አበሮች መሳሪያና ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያን ማከረባበትና የባህልም ውድቀት እንዲመጣ ማድረግና ሌሎችም የማህበራዊ ውድቀትና የአካባቢ መቆሸሽ… ወዘተ. ከቁጥር ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው።

ህወሃትም ስልጣን ላይ ሊወጣ የቻለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በወታደሩና በስለላው ውስጥ የዘረጋውን መረብ በመጠቀምና ወታደሩም እንዲፈርስ በመደረግ የተወሰነው በየፊናው እንዲበትን ከተደረገ በኋላ ነው። ይህም ማለት ህወሃት ስልጣን ላይ እንዲወጣ የግዴታ በአፄ ኃይለስላሴና በደረግ የአገዛዝ ዘመን የሰለጠነውና የተደራጀው የወታደርና የስለላ ኃይል መፈራረስ ነበረበት። ዋናው አፍራሹም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው። ይህም ማለት ህወሃት ብቻውን በማሸነፍ ስልጣን የወጣ ሳይሆን በጊዜው የነበረውን ድክመትና የአገር መፈራረስ በመጠቀም ነው። በእርግጥ ህዋሃት እታገላለሁ ብሎ በረሃ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ራሱ ተላላኪ በመሆን በአገር አፍራሽነት ስራው ሲንቀሳቀስ ነበር። በወታደሩ ውስጥም መረጃዎች የሚያቀርቡለት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ መኮንኖች ነበሩት። ከዚህ ሀቅና በጊዜው በደርግ ላይ ከየቦታው የተቃጣው ትግል ለወያኔ ስልጣን ላይ መውጣት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል። ስልጣንም ላይ ሲወጣ ማድረግ የሚገባውን ነገር ትዕዛዝ የተቀበለው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው። በአሜሪካንና በእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስቶች እሳቤ መሰረት እንደተቀሩት አገሮች ኢትዮጵያም እንደ አገር ወይም እንደ ህብረ-ብሄር((Nation-State) በአንድ ባንዲራ ውስጥ በመካተት መገዛት የለባትም። በፌዴራሊዝም ስም በብሄር በመሸንሸን በዚህ አማካይነት አለመተማመንና ትርምስ መፈጠር አለበት። ይህ ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና እንግሊዝ ዋናው ዓላማ። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ በመሰረቱ ራሳቸው ተግባራዊ አድርገነዋል የሚሉትን የሪፓብሊካንን አስተሳሰብ፣ ማለትም የግለሰብ መብትንና ነፃነትን፣ በህግ የበላይነት መተዳደርን፣ በአንድ አገር ውስጥ የሃሳብ መንሸራሸር እንዲኖር ማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ የተሟላ ዕድገት እንዲመጣ  አመቺ ሁኔታን መፍጠር የሚለውን የህብረ-ብሄር አገነባብ ሂደት ወይም መንገድ የሚፃረር ነው።  ከዚህም ባሻገር ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በቀጥታ ከዋሽንግተን በዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF)በዓለም ባንክ ረቆ የመጣ ነው። ይህ ፖሊሲ ደግሞ በተቋም መስተካከል ስም የተቋም መስተካከልን ያመጣ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ የተዛባ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረገ ነው። የኢኮኖሚ ፖሊሲው የአገር ውስጥ ገበያ((Home Market)እንዲያድግና እንዲስፋፋ የሚያደርግ አይደለም። ምክንያቱም የኢኮኖሚው ፖሊሲው ለአንድ አገር በተሟላ መልክ ለማደግ የሚያስፈልገው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የትናንሽና የማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ስለሚጎድሉትና ፖሊሲውም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የህዝባችንን አኗኗር በማንበብና በመተንተን መሰረታዊ ችግሩን ለመቅረፍ የተነደፈ ፖሊሲ ባለመሆኑ ነው። ባጭሩ ፖሊሲው ኢ-ሳይንሳዊ ከመሆኑ የተነሳ ድህነትን ከመቅረፍ ይልቅ ድህነትን የሚያስፋፋ፣ የተስተካከለ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ ያልተስተካከለ ዕድገትን ያመጣና በጣም ጥቂት የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በፈጠራ ሳይሆን በዘረፋ በሀብት እንዲናጥጥ ያደረገ ነው። ስለሆነም የህወሃት ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀብት ዘረፋ ላይ በመሰማራት ነው የናጠጡ ሀብታሞች ለመሆን የበቁትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማባለግ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ለማድረግ የቻሉት። በአጠቅላይ ሲታይ የወያኔ አገዛዝ በውጭ ኃይሎች የሚጠመዘዝና በከፋፈለህ ግዛው ፖሊሲ በህዝባችን ዘንድ መተማመን እንዳይፈጠር ያደረገና የኋላ ኋላ ለሚነሳ አደገኛ ኃይል አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ነው። በተለይም የውስጥ ለውስጥና በግልጽ በአማራው ክልል፣ በተለይም በወልቃይት ጠገዴ ያደርስ የነበረውና የሚፈጽመው ወንጀል የአማራውን ህዝብ የጎዳና በራሱ እንዳይተማመን ያደረገ ነበር። በብአዴን ስም የሚንቀሳቀሱ አማራዎችም በመሰረቱ የወያኔ ካድሬዎች ስለነበሩ ወያኔ የሚያዛቸውንና የሚፈልገውን ብቻ ነው ተግባራዊ ያደርጉ የነበረው። ስለሆነም በአማራው አክልል አንዳንድ ሆቴልቤቶች ከመሰራታቸው በስተቀር ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅምና የስራ መስክም ሊከፍት የሚችል ትናንሽና የማዕከለኛ ኢንዲስቱሪዎች ያልተቋቋሙት። ህዝቡንም ሊያሰባስቡ የሚችሉና የኑሮንም ትርጉም እንዲረዳው የሚያደርጉ ከተማዎችና መንደሮች ሊገነቡ አልቻሉም። ሌላው ቢቀር ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ከባላገር ሽንኩርትና ሌሎች አትክልቶችና እህሎች እያመጡ የሚሸጡበት የገበያ አዳራሽ አልተሰራላቸውም። እናቶችና አባቶች ከባላገር ሲመጡ የሚቀመጡትና የሚሸጡት ለጠራራ ፀሃይ የተጋለጠና በጣም የሚያቃጥል ቦታ ነው። በጥር፣ በየካቲትና እስከ ግንቦት ድረስ ባህርዳር ከተማው ውስጥ ሙቀቱ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስና በጣምም የሚያቃጥል ነው። በአካባቢውም መፀዳጃና ሻጪዎችም ውሃ ሲጠማቸው ውሃ ሊጠጡ የሚችሉበት የውሃ ቡንቧ በፍጹም አልተዘረጋም። በሌላ አነገጋር በዚያ ዐይነት ፀሃይ ከተቃጠሉ በኋላ ምንም ሳይፀዳዱና ውሃም ሳይጠጡ ነው እንደገና 10ና 20 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ ቤታቸው የሚደርሱት። በሌላ ወገን ደግሞ ለንዑስ ከብርቴውና ለብአዴን ካድሬዎች መዝናኛዎች ሆቴልቤቶች ተሰርተው እናያለን።  በውይይቱ ላይ ተጋብዞ ንግግር ያደርግ የነበረው የህወሃት ካድሬ የነበረው ደጉ አንዳርጋቸው ሊያሳምነን እንደሚሞክረው ሳይሆን በህዋሃት አገዛዝ ዘመን ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅምና ከድህነትም የሚያወጣው ምንም ዐይነት ዕድገት አልተሰራም። ደጉ አንዳርጋቸው ሊያሳምነን እንደሚሞክረው በኢህአዴግ ወይም በህወሃት የአገዛዝ ዘመን የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ይፈስ እንደነበረና ኢኮኖሚውም ያድግ እንደነበረ ነው። ይሁንና መዋዕለ-ነዋይ ይፈስ ነበር ሲል ምን ዐይነት መዋዕለ-ነዋይ ይፈስ እንደነበረና፣ ይህ ዐይነቱስ ከውጭ የሚገባ የመዋዕለ-ነዋይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያደረገውን አስተዋፅዖ ለማብራራትበፍጹም አልቻለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ በውጭ ኃይል የተደገፈና በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተና የአገሪቱን የውስጥ ገበያ ሊያሳድግ የሚችል የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ከውጭ አይገባም ነበር። የውጭ ኢንቬስተርም እንደ ኢትዮጵያ የመሰለው አገር ኢንቬስት ለማድረግ እፈልጋለሁ ብሎ ሲገባ የአገራችንን ኢኮኖሚ ሁለ-ገብ በሆነ መልክ ለማሳደግ ሳይሆን በጥሬ-ሀብት ማውጣትና በፍራፍሬና በአበባ በመትከል ላይ በመሰማራት ወደ ውጭ ለማውጣት እንጂ  አስተማማኝ የስራ መስክ በመክፈት የሰራተኛውም የመግዛት ኃይል እንዲያድግ ለማድረግ አይደለም። የህብረተሰብን ዕድገት፣ የሁለ-ገብ ኢኮኖሚን ዕደገትና መሰረቱንም ለመረዳት የማይችለው ደጉ አንዳርጋቸው በአገሪቱ ውስጥ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾች ይገቡ ነበር ሲለን ከላይ የዘረዘርኳቸውን ነገሮች መሰረት በማድረግ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው የብአዴን ከፍተኛ አመራር የነበረው፣ የህወሃት ካድሬና ኋላ ላይ ደግሞ በአቢይ ´የአገዛዝ ዘመን ለአጭር ጊዜ የውጭ ጉዳይ ምኒስተር የነበረው ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አስተሳሰብ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነና የኢኮኖሚን መሰረተ-ሃሳብና አንድ አገር በተሟላ መልክ እንዴት ማደግ እንዳለባት የሚያስተምረንን ፍልስፍናዊ አካሄድ የሚፃረር ነው። ሌላው ደጉ አንዳርጋቸው ሊያሳምነን የሚሞክረው በኢህአዴግ ወይም በህወሃት የአገዛዝ ዘመን በህዝባችን መሀከል መፈቃቀር እንደነበረና፣ ህወሃትም የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲን እንደማይከተል አድርጎ ነው። የጎሳን ፌዴራሊዝምን ተገን በማድረግና ሃይማኖትንም በመጨመር በህዝባችን ዘንድ አለመተማመንና እንዲያም ሲል ግጭት እንዲፈጠር ያደረግውና መሰረቱንም የዘረጋው በመለሰና በአቦይ ስብሃት ነጋ የሚመራው ሰይጣናዊ አገዛዝ ነው። ሀቁ ይህ ነው።

ስለሆነም በአቢይ አህመድና በህወሃት መሪዎች መሀከል ያለው ልዩነት የጥልቀትና(Intensity) የፍጥነት ካልሆነ በስተቀር ሁለቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ናቸው፤ በይዘት አንድ ናቸው ማለት ነው። ሁለቱም አማራውን በአንድነትና የኦርቶዶክስን ሃይማኖት በጭፍን የሚጠሉና መውደምም አለባቸው ብለው የሚያምኑና የታገሉ፣ አሁንም የሚታገሉ ናቸው። ሁለቱም በኢትዮጵያ ምድር ሁለ-ገብ የሆነና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም የተሟላ ዕድገት እንዳይመጣ የሚታገሉ ናቸው። ሁለቱም በዓለም አቀፍ የዘረፋ ሰንሰልት ውስጥ በመካተት የአገራችንን ሀብት እንዲዘረፍ የሚያደርጉና የነጭ ኦሊጋሪክው መደብ አገልጋዮች ናቸው። ሁለቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ የጠቅላላው አፍሪካዊው ጥቁር ህዝብ ጠላቶችና፣ አገራችንና አካባቢው በጦርነት እየተማሱ እንዲኖሩ የሚያደርጉ ናቸው። ይህም ስትራቴጂ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረ-አበሮቹ የሚመራ አንደኛው ዓለምን የማከረባበቻ ፖሊሲ ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮች የተቀረው የዓለም ህዝብ በጦርነት ሲያዝና ርስ በርሱ ሲዋጋ አገሩን ለመገንባት ጊዜ አይኖረውም፤ ኃይሉንና ያለውን ሀብት ይጨርሳል የሚል እምነት አላቸው፤ መመሪያቸውም ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ብቸኛው ኃያል መንግስት ሆኖ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የተቀሩትን የኔቶ አባል አገሮችን በማሰባሰብና የዓለም አቀፍን ስም የተከናነቡ ተቋማትን በመጠቀም አገሮችን የሚያተራምስው የተሟላ ዕድገት እንዳይኖራቸውና ራሳቸውን እንዳይችሉ ለማድረግ ነው። ድጉ አንዳርጋቸውና የተቀሩት ተሳታፊዎችና አዘጋጂዎች እንደ ልደቱ አያሌው የመሳሰሉት የአሜሪካንና የግብረ-አበሮቹን መሰሪህ አስተሳሰብ በፍጹም የተረዱ አይመስሉም።  በአጭሩ ህወሃት 27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በአቢይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና አገዛዝ የውጭ ኃይሎች አገልጋዮች ናቸው። ስለሆነም በይዘት በመሀከላቸው ምንም ዐይነት ልዩነት የለም ማለት ይቻላል።

አብዛኛውን ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ የምንሳተፍም ሆነ የማንሳተፍ፣ ወይም ከውጭ ሆነን የምንመለከት ቀደም ብለው የተደረጉ ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ በተለይም መጥፎ ድርጊቶችን ወደ ኋላ መለስ ብለን በማየት ድርጊቶችንና ተዋናዮችንም አንመረመርም። በተለይም ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ሁል ጊዜ የሚያሳብቡት በራሳቸው ላይ ሳይሆን፣ ለማዘናጋት ሲሉና እኛ ከደሙ ንጹህ ነን ብለው ሌላውን በማሳመን በዛሬውና በሚታየው ድርጊት ላይ ብቻ እንድንረባረብ ያደርጋሉ። ለማንኛውም ህወሃት የሚባለውና የኋላ ኋላ ላይ የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዚም ጉያ ስር በመውደቅና የእነሱም ታዛዥ በመሆን አገራችንን በጎሳ የሰነጣጠቀና ብሄራዊ ስሜትም እንዳይዳብር ያደረገው በዋናነት የሚጠየቅና ለክስም መቀረብ ያለበት ነው። ከደሙ ንጹህ ነኝ በማለት ሊያመልጥ የሚችል ኃይል አይደለም። ዛሬም ቢሆን የራሱን ነፃ አገር የመሰረተ ይመስል በመንደላቀቅና በመዝናናት፣ እንዲሁም በማስፈራራት የሚኖር ነው። እንደ ወልቃይት ጠገዴ የመሳሰሉትን ተፍጥሮአዊ ሀብት ያላቸውን አካባቢዎች የትግራይ አካል ናቸው በማለት በእሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ ታላቁን ትግራይ ለመመስረት የማያደርገው ጥረትና የማይሸርበው ተንኮል የለም። በዚህም የተንኮልና የጦርነት ስራው እንደ ብላክ ሮክ የመሳሰሉ የሶስተኛው ዓለምን፣ በተለይም የአፍሪካን የጥሬ.-ሀብት የሚቆጣጥሩና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም  በስተጀርባው አሉ፤ ግፋበት እያሉም ያማክሩታል። አንዳንድ የህዋሃት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑ በቀጥታ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ከአሜሪካኑ አምባሳደር ጋር ይወያያሉ። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምም አምባሳደር እሰከ መቀሌ ድረስ በመሄድ እንደ ደብረፅዮንን ያነጋግራቸዋል። የአውሮፓው አንድነት ተጠሪዎች ነን የሚሉትም ቤታቸው መቀሌ ነው። አቢይ አህመድና አገዛዙ ይህንን እያወቁ ዝም ብለው ያልፉታል። ለአሜሪካን አምባሳደር ማስጠንቀቂያ ከመስጠትና ድርጊቱ የአገርን ብሄራዊ ነፃነት የሚጥስ መሆኑን በማስረዳት በ48 ሰዓት ጊዜው ውስጥ አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ ዝም ብለው ይመለከታሉ። ይህ የሚያረጋግጠው አቢይ አህመድም ልክ እንደ ወያኔዎች የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አሽከርና  የብሄራዊ ነፃነታችንን አስደፋሪ መሆኑን ነው። የተቀመጠውም አገራችንን ለማስከበርና በተሟላ መንገድ ለመገንባት ሳይሆን የውጭ ኃይሎች አገልጋይ ሆኖ ለብዙ ዓመታት ስልጣን ላይ ለመቆየት ነው።

ወደ ተነሱት ነጥቦች ጋ እንምጣ። “ሰላም ይስፈን፣ ጦርነት ይቁም፣ ግፋዊ አገዛዝ ያክትም”  የሚሉትን ነጥቦች ስንመለከት ለእነዚህ ቀውሶች መሰረት የሆኑትና ዋናው አክተሮች በሚገባ አልተነተኑም። ይህንን የውይይት የኦንላይን መድረክ ያዘጋጁት ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ሲታይ በፖለቲካው ውስጥ እንሳተፋለን የሚሉ ኃይሎችንና ድርጅቶችን ስንመለከት በመንግስት ላይ ያላቸው አመለካከት ግልጽ አይደለም። የመንግስቱን መኪና ስልጣንን ከጨበጡት ሰዎች ለይተው ነው የሚያዩት። በተጨማሪም የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠሩትን፣ ወታደሮች፣ ጄኔራሎች፣ የስለላ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ መዋቅሩና ሌሎችም አገዛዙ የሚገለገልባቸው ተቋሞች በሙሉ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን የተገነቡና ለደርግ የተላለፉና፣ የኋላ ኋላ ላይ ወያኔ ስልጣንን ሲቆጣጠር ለራሱ በሚስማማ መልክ የጭቆና መሳሪያ አድርጎ የገነባው ነው። አቢይ አህመድም ይህንን መሰረት በማድረግ ነው እያረቀቀውና የህዝብ መጭቆኛና አገርን ማፈራረሻ መሳሪያ እያደረገ ለመምጣት የበቃው። የመንግስቱም መኪና በቀጥታ የሚቆጣጠሩት ጄኔራሎችና መኮንኖች፣ እንዲሁም የስለላ ሰዎችና የፍድርቤትንም ዳኞች ጨምሮ ሰፋ ያለና የጠለቀ ምሁራዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው። ይህም ማለት በራሳቸው ህሊናና ውሰጠ-ኃይል በመመራት ለአገራችንና ለህዛብችን የቆሙ አይደሉም። ምሁራዊ ብቃትም ስለሌላቸው ውስጣዊ ነፃነት የላቸውም። ይህም ማለት የራሳቸው ህሊና ስለሌላቸው ወይም በህሊናቸው ማገናዘብ ስለማይችሉ በህገ-መንግስት ውስጥ የሰፈኑትንና የጠቅላይ ምኒስተሩ ዋና ተግባር ምን እንደሆነ የማይረዱ ናቸው። የሚመስላቸውም አንድ ሰው ጠቅላይ ምኒስተር እንደመሆኑ መጠን የፈለገውን ማድረግ ይችላል፤ ሲያዘንም መታዘዝ አለብን ብለው የሚያምኑ ናቸው። በህገ-መንግስቱ ውስጥም የሰፈኑትን ፓርሊያሜንት፣ በፍርድቤትና በኢክስኩቲቩ መሀከል ያለውን የስራ-ክፍፍል የማይረዱና፣ እንደማንኛውም ምኒስተሮች ራሱ ጠቅላይ ምኒስተሩም በፓርሊያሜንቱ የመጠየቅ ግዴታ እንዳለበት የተገነዘቡ አይመስሉም። ሰልሆነም ጠቅላይ ምኒስተሩ በህዝባችን ላይ ጦርነት ማካሄድ አለባችሁ ብሎ ሲያዛቸው ዝም ብለው የሚቀበሉና ትዕዛዝም በማስፈፀም የአንድን አገር ህዝብ በጎሳና በሃይማኖት በመከፋፈል ጦርነት የሚያካሂዱና ወጣት ልጆችን በጦርነት እየተጋፈጡ እንዲያልቁ የሚይደርጉ ናቸው። በአጭሩ እነ ልደቱ አያሌው ባካሄዱት የኦንላይን ውይይት ላይ ለሰላም እጦት፣ ለግፍ አገዛዝና ለጦርነት መካሄድ ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ በስርዓትና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ተተንትኖ የቀረብ አይደለም። ስብሰባውም ላይ የተካፈሉት በሙሉ ምሁራዊና ሳይንሳዊ መሰረትና ግንዛቤ የሌላቸው ስለሆኑ ነገሮችን እየተነተኑ ለማቅረብ የሚችሉ አይደሉም።

ሌላው እንደዚህ ዐይነት ዝግጅት ሲካሄድ የአሰራር ስልቱና ርዕዮተ-ዓለሙ በሚገባ መታወቅ አለባቸው። ራሳቸው የውይይቱ ጋባዥዎች ተራማጆች ይሁኑ አይሁኑ፣ ቀኞች ይሁኑ አይሁኑ፣ ሊበራሎች ይሁኑ አይሁኑ፣ ፋሽሽቶች ይሁኑ አይሁኑ የሚታወቅ ነገር የለም። በደፈናው በፖለቲካ ስም የሚነግዱ ናቸው። እንደሚታወቀው ፖለቲካ እንደማንኛውም የሶሻል ሳይንስ ዘርፍ ራሱም ሳይንስ ሰልሆነ ፖለቲካዊ ስብሰባዎችም ከሳይንስ አንፃር በመታየት ነው ልዩ ልዩ አጀንዳዎች መተንተን ያለባቸው። ፖለቲካ ሳይንስ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ሲገባና፣ የፖለቲካ ዋናው መሰርተ-ሃሳብም ከነፃነትና ከመብት ጋር የተያያዘ ሰለሆነ መሰረተ-ሃሳቡም ዲስፖቲያዊ አገዛዝን ወይም የአንድን ገለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት በመቃወም የፈለቀና፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ ስልጣንንም የጨበጠ ሁሉ በህግ ፊት እኩል ሆኖ የሚታይና የሚጠየቅም መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም በላይ ፖለቲካ አንድን አገር በተሟላ መልክ መገንቢያና ሰላምም አስፋኝ መሳሪያ ነው። ለባህል ዕድገትና ለስነ-ልቦና መጠንከር በማገልገል ብበአንድ አገር የሚሆን ህዝብ በመፈቃቀር የሚርበት ልዩ ዐይነት ሳይሳዊ መሳሪያ ነው። ብለኢአ አነጋገር ፖልቲካ ማለት የወንበዴዎች መሳሪያ ሳይሆን ቅዱሳዊና ሳይንስዊ አስተሳሰብ ነው፤ ሰይጣናዊ ስራ የሚሰራበት አይደለም። ጠቅላይ ምኒስተርም ሲባል የሌሎች ምኒስተሮችን ስራና ኃላፊነት የሚቆጣጠርና የህዝብም አገልጋይ የሆነ እንጂ ልዩ መብት ያለው አካል አይደለም፤ ልዩ ፍጡርም አይደለም። እንደማንኛውም ሰው ሰው ነው። ይህም ማለት አንድ ጠቅላይ ምኒስተርና አገዛዙ በህዝብ ሀብትና በሚከፍለው ቀረጥ የሚተዳደሩ ስለሆነ ዋናው ተግባራቸው አንድን አገርና ህዝብ ማገልገልና ብሄራዊ ነፃነቱን ማስከበር ነው። ራሳቸውም ሀብት ፈጣሪዎች ስላልሆኑና በቀጥታም በምርት ክንዋኔ ውስጥ የሚሳተፉ ስላልሆነ ተጠቃሚዎች እንደመሆናቸው መጠን የግዴታ የህዝብን ድህንነት የሚጠብቁና አገልጋዩም ናቸው ማለት ነው። ከዚህ አጠር መጠን ያለ አቀራረብ ስንነሳ ልደቱ አያሌውና ሌሎች ተጋባዦች የመንግስትን ሚናና የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩት ሰዎች ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን ያልተረዱ መሆናቸውን ለማስገንዘብ በፍጹም አልሞከሩም። ዋናው አዘጋጁም ሆነ ጀዋርና ሄዝቃይስ፣ ደጉ አንዳርጋቸውና ሌሎችም ተጋባዦች ምንም ዐይነት ምሁራዊ መሰረትና ጥራት የሌላቸው ናቸው። ስለሆነም እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የመናገር መብትና እንደ አማራጭም ሆነው የመቅረብ መብት የላቸውም። አንዳንዶች በዋናነት የተሳተፊት ግለሰቦች ራሳቸው በአገራችን ውስጥ አፍጠው አግጠው ለሚታዩት ችግሮች በሙሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ናቸው። ልደቱ አያሌው፣ ደጉ አንዳርጋቸውና ጀዋር መሀመድና አሉላ ሰለሞን የሚባለው የትግራይ ተወላጅ፣ ሌሎችም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚያምኑና በእሱም ድጎማ የሚኖሩ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ከአቢይ አህመድ ፋሽሽታዊ አገዛዝ ለመላቀቅ የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እነዚህን ሰዎች እንደ አማራጭና የተሻሉ ናቸው ብሎ ማመንና መውሰድ የለበትም።

በአጠቃላይ ሲታይ ይህ ዐይነቱ የኦንላይን ስብሰባ የወያኔን የ27 ዓመት አገዛዝ ከደሙ ነፃ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን የተደረገ ዝግጅት ሲሆን፣ ወያኔ የጣለውን የጥላቻ መርዝ፣ የርስ በርስ አለመተማመን፣ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት በወያኔ ካድሬዎች የተካሄደውን የሀብት ዘረፋና ወደ ውጭ የማሽሸ ተግባር ያነሳና የተወያየ አይደለም። የአቢይ አህመድ አገዛዝም የወያኔ አገዛዝ የዘረጋውን የጥላቻና አገርን የመከፋፈል ስልት በመጠቀም ጥልቀትና ስፋት እየሰጠው እንደመጣ በፍጹም ግንዛቤ ውስጥ የተገባ አይደለም። አቢይ አህመድም ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ጽፈው የሚሰጡትን የተቋም ማስተካክያ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርግና ከአንዴም ሁለቴም በላይ የኢትጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር የመግዛት ኃይሉ ዝቅ(Devaluation) እንዲል እንዳደረገ፣ ከሰባት ወራት ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት ኃይሉ በጠያቂና በአቅራቢ የገበያ ህግ ብለው በሚጠሩት ፈሊጥ(Free Floating)ተግባራዊ በመሆኑ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን እንዳስከተለና ሰፊውንም ህዝብ እንዳስመረረው አልተተነተነም።በተለይም ስለድህነት መስፋፋት በተደጋጋሚ ያነሳው ጀዋር መሀመድ ዛሬ በአገራችን የሚታየው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የስራአጥ  መብዛት፣ የዋጋ ውድነትና ድህነትም መስፋፋት ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ለማብራራት በፍጹም አልሞከረም። ለአንድ ነገር መከሰት ምክንያት እንደሚኖረው ሁሉ ዛሬ በአገራችን ምድር ለሚታየው ድህነትና የኑሮ ውድነት፣ በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚ ቀውስ፤ በቂ የስራ መስክ ሊከፍት የሚችል የኢኮኖሚ ዘርፍ አለመዘርጋትና፣ የሰፊውም ህዝብ የመግዛት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ መዳከምና ድህነትና ኋላ-ቀርነት መስፋፋት ዋናው ምክንያት እስካልታወቀ ድረስ ድህነት ተስፋፍቷል እያሉ ማውራቱ እንደመፍትሄ ሊሆን አይችልም። የግዴታ የችግሩ ዋና ምክንያት መታወቅ አለበት። የችግሩ ዋና ምንጭ ጠቅላላው አገዛዝ ሲሆን፣ ካለምንም ምሁራዊ ጥናትና ክርክር ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነት እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅቷል። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ በውጭ ኃይል የማይጠመዘዝና የማይታዘዝ፣ በራሱ ህሊናና ዕውቀት የሚገዛ አገዛዝና ምሁራዊ ኃይል ያስፈልጋል። ከዚህም በመነሳት በጠቅላላው የመንግስት መኪናዎችና የሚቆጣጠሩትም ሰዎች ንቃተ-ህሊናቸው በዳበረና ዕውቀት ባላቸው ሰዎች መመራት አለበት።  ዋናው የአገራችንም ችግር ብሄራዊ ባህርይ ያለው፣ የነቃና በጥልቀትና በስፋት ማሰብ የሚችል የተደራጀ ምሁራዊ ኃይል ለማዳበር አለመቻላችን ነው። ይህ ዐይነቱ ክፍተትም ስላለ የውጭ ኃይሎች አገልጋዮች የሆኑ እንደ ህወሃትና የአቢይ አህመድ የመሳሰሉ የብልጽግናን ስም የተከናነቡ ስልጣንን በመያዝ ለሰላም እጦት፣ ለጦርነት መስፋፋትና ለግፋዊ አገዛዝ ምክንያት በመሆን ታሪክ እንዳይሰራ እንቅፋት ይሆናሉ። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግበረ-አበሮችም እንደዚህ ዐይነት ኃይሎችን ብቻ ነው የሚፈልጉት። እንደ ኢብራሂም ትራኦሬ የመሳሰሉ በራሳቸው የሚተማመኑ ግለሰቦች ስልጣንን ሲጨብጡና ጥፉልኝ ሲሏቸው መንጫጫት ይጀምራሉ። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ ውጥቅንጥ ሁኔታ ለመወጣት ከፍተኛ ትንቅንቅና ዝግጅት ማድረግ ያለብን ይመስለኛል። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                                      fekadubekele@gmx.de

                                                             www.fekadubekele.com

https://www.youtube.com/watch?v=dsZgbXmpv-k

https://www.youtube.com/watch?v=bAv1XBvLbME

https://www.youtube.com/watch?v=hecdpm35K4Q

https://www.youtube.com/watch?v=vm1ohq9WeAA