[gtranslate]

 

ፖለቲካ እንደዕምነትና እንደ መርህ !

                                              ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                  ህዳር 05፣ 2019

መግቢያ

ከአርባ ዓመት በላይ በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የተካሄደውን ውዝግብና የእርስ በእርስ መጨራረስ፣ ከዚያም አልፎ የብዙ መቶ ዓመታትን ባህላዊ ክንውንና ውጤት እንዲፈራርስ ማድረግ ይህ ሁሉ ግፍ የደረሰው ካለምክንያት አይደለም። ስለተወሳሰበው የህብረተሰብ ዕድገት ታሪካችንና፥ እንዲያም ሲል ስለ ሰውልጅ ያለን ግንዛቤ አልቦ ስለሆነ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በየታሪክ ኢፖኩ ስልጣንን የጨበጡት ነገስታትና ህዝባችንም አገራችን እንደማህበረሰብ እንድትገነባ ያደረጉትን በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጸውን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባታችን ወይም ደግሞ ወደ ኋላ ዞር ብለን ለመመርመር ባለመቻላችን ነው። አንድ አገር  ታሪክ የሚሰራበት መሆኑና ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ የሚሸጋገር መሆኑ ብቻ ሳይሆን አባቶቻችንና እናቶቻችን በጊዜው በነበራቸው ዕውቀትና አገራቸውን ከጠላት ወራሪ ኃይል በቆራጥነት ተከላክለው ያስረከቡንን አደራ በመዘንጋታችንም ጭምር ነው።

በመሰረቱ ፖለቲካ የሚያጨራርስ፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርግና በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ በሙሉ ኃይሉ ቂም በቀል የሚወጣበትና ባህልንና ታሪክን እንዳለ የሚያወድምበት መሳሪያ  አይደለም። ያለፈውን በፖለቲካ ስም የተካሄደውን በብዙ ሚሊዮን ህዝብ ላይ የደረሰውን ሰቆቃና የአገር ውድመት ታሪካችንን ካወጣሁና ካወረድኩኝ በኋላ ፖለቲካ በዚህ መልክ መካሄድ ያለበት ጉዳይ ነው ወይ?  የሚለውን ለመመርመርም ሆነ ለማጥናት ብዙ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችንና ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ የአገር ግንባታ መሳሪያዎችን ካገላበጥኩኝ  በኋላ በአንዳቸውም መጽሀፍ ውስጥ  ፖለቲካ እኛ አገር በተካሄደው መልክ መካሄድ እንዳለበት የሚያረጋግጥ ማስረጃ በፍጹም ላገኝ አልቻልኩም። ታዲያ አገርን ስታወድም፣ ባህልንም ስታፈራርስና፣ ሰውንም ስትጨርስ ብቻ ነው ፖለቲካ የሚባለው ነገር ትርጉሙ የሚታወቀው የሚል የተጻፈ ነገር ከሌለ የእኛ አገር የፖለቲካ ተዋናይ ነን ባዮች ከየት አምጥተው ነው ይህንን ሁሉ እልቂት እንዲደርስ ያደረጉትና ዛሬ የምናያትን አስቀያሚ አገር እንድንረከብ ያደረጉን? ብዬ ስጠይቅ መልሱ ቀላል ነው። በብዙ ፈላሳፋዎች፣ የህሊናና የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደተረጋገጠው በፖለቲካ ስም አሳበው በህዝብ ላይ እንደዚህ ዐይነቱን ጭንቅላትን የሚዘገንን ድርጊት የሚፈጽሙ ጭቅንላታቸው ያልበሰለ፣ ያልተገራና መጓዝ ያለበትን የንቃተ-ህሊና ጉዞ ደረጃ  በደረጃ ያልተጓዘ ሰዎች ብቻ የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነ ለማረጋገጥና ለመገንዘብ ችያለሁ። በተጨማሪም ጭንቅላታቸው የሰው ልጅ በሙሉ ሊኖር የሚችለውን ባህርይ ያልያዘ፣ ወይም በጭንቅላታቸው ውስጥ ያልተቀረጸ ከሆነ እነዚህ ዐይነት ሰዎች ተግባራቸው በሙሉ ሰውን ከማሰቃየትና ከመግደል በስተቀር ሌላ የሚታያቸው ነገር የለም።

በተለይም ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብና ከሱ ጋር የተያያዙ በተለያየ መልክ የሚገለጹ የፍትህ ጥያቄዎች  ግንዛቤ እስኪያገኙ ድረስና መልስም እስኪሰጣቸው ድረስ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከፍተኛ ትግል እንደተካሄደ ይታወቃል። የፍትህ ጥያቄ በጥንት በግሪኩ የስልጣኔ ዘመን በእነ ሶክራተስና ፕላቶ፣ እንዲሁም በአርስቲቶለስ የተተነተነና መሰረታዊ ነገር ቢሆንም፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍትህነትትን ለማረጋገጥና መልስ ለመስጠት  እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ድረስ በአውሮፓው ምድር ከፍተኛና የማያቋርጥ ትግል ተካሂዷል፤ አሁንም ቢሆን እየተካሄደ ነው። ይሁንና ግን በፖለቲካ ስም ተሳቦ አልፎ አልፎ በየአገሮች ውስጥ ግብ ግብ ቢፈጠርም እንደኛ አገር ምርር ባለ መልክ የተካሄደና ፖለቲካ የሚባለው ነገር በመጣመም ወይም ከፍተኛ ግንዛቤ ባለማግኘት ወደ አገር አፍራሽ ፕሮጀክትነት የተለወጠበት ሌላ አገር የለም ብሎ መናገር ይቻላል። በተለይም ፖለቲካ ወደ ቂም-በቀል መሳሪያነትና ወደ እልከኝነት በመለወጥ ዲሞክራሲያዊ ውይይትና ምሁራዊ ክርከር እንዳይደረግ መሰናክል የሆነበት እንደኛ አገር ያለ አገር የለም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የፖለቲካ ግንዛቤ ልክ እንደኛ አገርና በእኛ የፖለቲካ ተዋናያኖች በተካሄደው ዐይነት በአውሮፓ ምድርም ይህ ዐይነቱ በጭንቅላቱ የቆመ ግንዛቤ ቢኖር ኖሮ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ሁለ-ገብ ዕድገትና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባልታየና ባልዳበረ ነበር። እንደዚሁ እኛም እዚህ መጥተን ጥገኝነት ጠይቀንም ሆነ ወይም በሌላ አጋጣሚ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ አግኘተን አነሰም በዛም የተደላደለና የሰላም ኑሮ መኖር ባልቻልንም ነበር።፡

ከዚህኛው የመጨረሻ አረፍተ ነገር ስነሳና በጠቅላላው በፖለቲካ ስም በአገራችን ምድር የተካሄደውን በንፅፅር የጥናት መነፅር ስገመግም የምደርስበት ድምደማ ጭንቅላታችን አንድ ችግር እንዳለበት ነው። በተለይም አንድ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ሰው የህይወት ታሪኩ ንጹህ መሆንና ከማንኛውም ወንጀልና ቂም-በቀል ወይም ዕቡይ አስተሳሰብ የጸዳ መሆኑን በስነ-ምግባር ኮሚቴ መጣራትና አገርን ሚዛናዊ በሆነ መልክ ለማስተዳደር ብቃት እንዳለው ወይም እንደሌለው   መረጋገጥ  አለበት። አንድን አገር የስልጣኔ ባለቤትና ህዝቡም ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ ተጠብቆ ካለአንዳች ፍርሃት የሚኖርባት አገር ለመገንባት ከተፈለገ  የፖለቲካ ስልጣንን ተረክቦ የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል የሚወስን ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የህይወት ታሪኩና ያበረከተው አስተዋፅዖ የግዴታ መመርመር አለበት። በተለይም ስለፖለቲካ ያለው ግንዛቤና ምህራዊ ብስለቱም የግዴታ መመርመርና፣ እንዴትስና በምን መሳሪያና መመሪያ ጠንካራ ማህበረሰብ እንደሚገነባ መረጋገጥ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድ ህዝብ እፎይ ብሎ ሊኖር፣ ሊሰራና ሊፈጥር የሚችለው።

   ፖለቲካ  ምሁራዊ ጥልቀትንና ታሪካዊ ግንዛቤን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው!

የፖለቲካ ፈላስፋዎችን መጻህፍት፣ ፖለቲካን ከሃይማኖታዊ አሰተሳሰብ ጋር በማገናኘት ሰለፖለቲካ የተነተኑና፣ እንዲሁም ለፍትህና ለዕኩልነት የታገሉ የተለያየ የርዕዮተ-ዓለም ግንዛቤ ያላቸውን፣ በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት በመካሄድ ላይና ከተካሄደ በኋላም ብቅ ብቅ በማለት ይታዩ የነበሩ ኢ-ፍትሃዊ  የሆኑ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎችን አንስተው  የታገሉና ያስተምሩ የነበሩ ታላላቅ ምሁራንን የህይወት ታሪክ ጨረፍ ጨረፍ አድርጎ ለተመለከተ እነዚህ ሰዎች የቱን ያህል የጠለቀ ዕውቀት እንደነበራቸው መገንዘብ ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጭንቅላታቸውም ከማንኛውም ዐይነት ዕቡይ ተግባር የፀዳና ህልማቸው በሙሉ ፍትሃዊነትንና ዕኩልነትን ለማስፈን ብቻ ነበር። ከዚያም በኋላ በአብዮት ስም የተካሄዱትን ክንዋኔዎችና  የተዋናያኖችንም የህይወት ታሪክ ስንመመረምር የምንደርስበት ድምደማ እነዚህ ምሁራን ስልጣንን ከመያዝ ባሻገር አገራቸውን ታላቅና የሳይንስና የቴክኖሎጂ  ባለቤት አድርጎ ለመጭው ትውልድ አሳልፎ መሄድ ነው።

በራሺያ ውስጥ አብዮታዊ እንቅስቃሴን የጀመሩት እንደ ፕሌክሃኖቭና ተማሪው ሌኒን፥ እንዲሁም ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ አብዮታዊ ታጋዮች ከአገራቸው የህብረተሰብ ታሪክ አልፈው የአውሮፓውን የህብረተሰብና የባህል ታሪክ በደንብ ጠንቅቀው ያወቁ ነበሩ። ስለሆነም ትግል ሲጀምሩ የአገራችውን ኋላ-ቀር ሁኔታ በመረዳት እንዴት አድርገው ከኋላ በመነሳት አገራቸውን በኢንዱስትሪና በዘመናዊ ኢንስቲቱሽኖች የሚገለጽ የዕድገት ደረጃ ላይ ማድረስ እንችላለን የሚለውን በማውጣትና በማውረድ ነበር። በተለይም ህብረተሰቡ በተለያየ የስራ-ክፍፍል ባልተሰማራበትና የቴክኖሎጂው ዕድገት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝበት አገር ህብረተሰብአዊ ለውጥ በምን ዐይነት መልክ መምጣት እንዳለበት አነሰም በዛም የተገነዝቡና፣ በኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ላይ የጠለቀ፣ በተለይም ደግሞ ሰለካፒታሊዝም ዕድገትና ሂደት ከፍተኛ ግንዛቤ የነበራቸው ስለመሆናቸው የህይወት ታሪካቸውንና ተግባራዊ ያደረጉትንም አጠቃላዩን ፖሊሲ ለተመለከተ ሊገነዘበው ይችላል። ወደ ቻይናም ስንመጣ በ1911 ዓ.ም የሪፑብሊክ ምስረታ ከከሸፈ በኋላ የተደረሰበት ውሳኔ ረጅም ጉዞን በመጓዝ በቻይና ምድር ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ለውጥ ማምጣት ነበር። በተለይም የቻይናን አስቸጋሪ ሁኔታና በእንግሊዝ በኦፕየም ጦርነት የደረሰባትን ጥቃትና የጃፓንን ወረራና የደረሰባቸውን አሳፋሪና የተገዥነት መንፈስ የተረዱት እነ ማኦ ሴቱንግ የመሳሰሉት ታላላቅ መሪዎች የአገራቸውን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የካፒታሊዝምን ዕድገትና  ውስጣዊ እንቅስቃሴና ሎጂክ በደንብ በመረዳት ነው ትግላቸውን የጀመሩት። ትግላቸውም አንድ ታላቅ አገር ለመገንባትና የሰፊውን ህዝብ ኑሮ በማሻሻል ለመከበርና ለመፈራት ነው።   በዚያን ጊዜ ወደ አምስት መቶ ሚሊዮን የሚሆነውን ህዝብ ነፃ ለማውጣትና ተከብሮ እንዲኖር ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ ህዝቡን ማደራጀትና በፖለቲካ ማንቃት ነበር። በተለይም የፊዩዳል ስርዓት በተንሰራፋበትና ድርጅታዊ መዋቅር በሌለበትና የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኝበት አገር የነበረው አማራጭ ህዝቡን በማደራጀትና በማንቃት ማንነቱን እንዲያውቅ ማድረግ  ነበር። አንድን አገር ታላቅ አድርጎ መገንባት የሚቻለውም ህዝብን ሲያደራጁና የፖለቲካ ነቃተ-ህሊናውን ከፍ ሲያደርጉ ብቻ እንደሆነ ለእነ ሌኒንም ሆነ ለእነ ማኦ ሴቱንግ  ግልጽ ነበር። እነዚህ ሁሉ ምሁራንና አብዮትን ያካሄዱ መሪዎች መቋጠሪያ የሌለውን ዕልቂት በመፈጸም ነው ወይ አገራቸውን መገንባት የቻሉት? በመከፋፈልና  በቂም-በቀልናዐይንህን አላይም በማለት ነው ወይ ህብረተሰባቸውንና አገራቸውን መገንባት የጀመሩት ወይ? በፍጹም አይደለም። ከአንዳንድ እርምጃዎች በስተቀር ሙሉ ኃይላቸውን ያስተባበሩትና በአገር ወዳድነት ስሜትና እንዲሁም በምሁራዊ ጥልቀት በመመራት ነው አገራቸውን በሁሉም አቅጣጫ ለመገንባት የቻሉትና የተከበረና የሚፈራ ህዝብ ያዳበሩት።

አንድን አገር በፀና መሰረት ላይ ለመገንባትና ህብረተሰብን ለመለወጥና ዘመናዊ ለማድረግ ከጠለቀ ዕውቀት ባሻገር የግዴታ የሞራል ብቃት እንዲኖር ያስፈልጋል። ጭንቅላት በልክስክስ ነገሮች ያልተጠመደ ሲሆን ብቻ ነው  አንድ ምሁር ወይም ድርጅት በሙሉ ኃይሉ እራሱን በማዘጋጀትና ሌላውን በማደራጀትና ምሳሌ በመሆን አገርን በጸና መሰረት ላይ ለመገንባት የሚችለው። ሰለሆነም ክምሁራዊ ብቃት ባሻገርም የግዴታ የሞራል ብቃት ለአገር ግንባታ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት የራሽያም ሆነ የቻይናው፣ እንዲሁም  የምዕራብ አውሮፓንና የአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ አገሮችን ታሪክና ያሉበትንም ሁኔታ ያረጋግጣል። በተለይም በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ላይ በዕድገታቸው ኋላ የቀሩ አገሮችን ታሪክና ዛሬ የደረሱበትን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ስንመለከት አገዛዞችም ሆነ ምሁራኑ እኛም ከሌላው የምናንስበት ነገር የለም፣ እንደሌላው አገርም አኩሪ ታሪክ የነበረን ነው በማለት ነው ተባብሮ በመነሳትና በአርቆ-አስተዋይነት አገራቸውን ለመገንባት የቻሉትና ዛሬ የሚፈሩበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት። በማጎብደድና በመለማማጥ አይደለም አገራቸውን ለመገንባት የበቁት።

ወደ እኛ አገር ስንመጣ ያለው ችግርና በተለይም ያለፈውን የአርባ ዓመት የፖለቲካ ታሪክ ስንመረመር ከተወሰነ ጊዜ በሰተቀር ፖለቲካ የሚባለው ታላቅ የአገር መገንቢያ መሳሪያ ወደ ቂም-በቀልነትና ወደ አገር አፍራሽነት የተቀነሰበት ጽንሰ-ሃሳብ እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። በተለይም ደግሞ እራስን ስልጣን ላይ ለማውጣት ሲባል ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው ኃያል መንግስት ተገዢ በመሆን አገርንና ታሪክን ማፈራረሻ የሆነበት ፓለቲካ የሚባለው ትልቅ ግዙፍ ነገር ከእኛ አገር በስተቀር እንደዚህ የወረደበትና የረከሰበት አገር በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። ይህ ዐይነቱ የሞራል ዝቅጠት ደግሞ የታየበት የሶስት ሺህና ከዚያም ዘመን በላይ የሆነ ታሪክ ያላት አገር ናት በሚባልባት አገር ነው። በተለይም ደግሞ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደ አገርና እንደ ማህበረሰብ ወደዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ እናቶቻችንና አባቶቻችን ከውጭ የመጣባቸውን ወራሪ ኃይል መክተውና በድል ተወጥተው ያስረከቡንን አገር  ማፈራረስና ባህልና እሴት እንዲወድሙ ማድረግ  የሚያረጋግጠው የቱን ያህል የታሪክን ውጣ-ውረድነት ለመገንዘብ አለመቻላችን ነው። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ታሪክ ውጣ ውረድ የሞላበት ነው። የአንድ አገር ህዝብና በተለያየ ዘመን ስልጣንን የሚጨብጡ ኃይሎች እራሳቸውን በራሳቸው እስኪያገኙና ታሪክን ለመስራት እስኪገለጽላቸው ድረስ ረጅም ጉዞን መጓዝ አለባቸው። አንድ አገርና በተለያዩ ነገሮች የሚገለጹ ሰው ሰራሽ ነገሮች  ከላይ በአንዳች ኃይል ተዋቅረውና ተስተካክለው ለአንድ ህዝብ እንደቡራኬ የሚሰጡት ሳይሆኑ በአንድ አገር ውስጥ በሚኖር ህዝብ አርቆ-አስተዋይነትና ምሁራዊ ብቃትነት ነው ሊገነቡ የሚችሉት። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ አገር በጸና መሰረትና ጥበባዊ በሆነ መልክ ያልተገነባና ህዝቡም ተዝረክርኮ የሚኖር ከሆነ ምክንያቱን ማወቅ የምሁራን ተግባርና ሞራላዊ ግዴታ ነው። በተለይም የአንድን አገር ታሪክና በየጊዜው የነበረውን የህዝብና የአገዛዞች ንቃተ-ህሊና ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ የሚደረግ ትግልና አስቸጋሪውን ሁኔታ ወደ ጭቆናና ትምክህተኝነት ለውጦ አጉል ግብ ግብ ውስጥ መግባት ይህ ጉዳይ የሚያረጋግጠው ከፍተኛ ምሁራዊ ክፍተት እንዳለ ነው። በሌላ ወገን ግን የአገራችን ታሪክ አስቸጋሪ የሆነውን ያህል ባህላዊ ክንዋኔና ለውጦች እንደተካሄዱ መገንዘብ እንችላለን። በተለይም ደግሞ ከትውልድ ትውልድ እየተሻሻለ የመጣው የግዕዝ ፊደልና የአማርኛ ስነ-ጹሁፍ፣ እንዲያም ሲል ውብ ውብ ዘፈኖችና የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ የምግብ ዐይነቶች መፈጠርና እነሱን መመገብ የሚያረጋግጠው እነዚህ ነገሮች በሙሉ የረጅም ጊዜ የባህልና የጭንቅላት ስራ ውጤቶች ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የግዕዝ ፊደልም ሆነ የአማርኛ ቋንቋ መዳበርና ጠቅላላውን አገራችንን ማዳረስ፣ እንዲሁም የተለያዩ የምግብ ዐይነቶችና ሙዚቃዎች በመፈጠር ጠቅላላውን አገር ማዳረስ ከጭቆና፣ አንዱ የበላይነቱን በሌላው ላይ ለማስፈን ካለው ፍላጎት ጋር የሚያያዙ ሳይሆኑ ይህ ዐይነቱ የባህል ክንዋኔ መስፋፋት የሚያረጋግጠው የባህልን ውስጣዊ-ኃይልና የሰውንም ልጅ ነገሮችን የመረዳትና የማዳበር ኃይል የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህ ስንነሳ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገቡ በእልክና በቂም-በቀልነት በመወጠር ለመጨረሻው ፍልሚያ(Final Solution) መነሳትና አገርን ለማውደም መፎከር የሚያረጋግጠው  የፖለቲካ ተዋንያኖችንና በነፃ አውጭ ስም የሚነግዱትን ድርጅቶች የጭንቅላት ሁኔታ ነው። ጭንቅላታቻው ያልዳበረ፣ ማለፍ ያለበትን ምሁራዊ ሂደት ያልተጓዘና፣ አገርን ከመሸጥና ከማፈራረስ በስተቀር ታሪካዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የማይችል መሆኑን ነው።

ይህንን ሁሉ ስናገናዝብ የምንደርስበት ድምዳሜ  ዋናው ችግራችን ትላንትናም ሆነ ዛሬ ጭንቅላታችን ያለመዳበሩንና ክፉውን ከደጉ፣ ሰውን ከሚጎዳውና ክማይጎዳው መለየት የማንችል ብቻ ሳንሆን ህሊና የሚባለው ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊውና ሰው ሰው መሆኑን የሚያስገነዝበው ነገር ጭንቅላታችን ጋር በፍጹም አይ አልተፈጠረም ወይም ደግሞ ተፈጥሮ በማይታወቅ ምክንያት እንደጠፋ ነው መገንዘብ የሚቻለው።

ወደ ምዕራብ አውሮፓ የዕውቀት ዕድገትና የአገር ግንባታ ታሪክ እንደገና  ስንመጣና በተለያየ የታሪክ ኤፖክ የፈለቁትንና የዳበሩትን ዕውቀቶች ስንመለከት በተለያየ መልክ የሚገለጹት ዕውቀቶች በሙሉ የህብረተሰብን ጥያቄ ከመመለስና አገርን ከመገንባት አኳያ ነው መዳበር የቻሉት። ይሁንና ግን ተፈጥሮንም ሆነ የፖለቲካን፣ የኢኮኖሚንና የማህበራዊ ፍትሃዊነትን በሚመለከት ጉዳይ ላይ በተለያዩ ምሁራን ዘንድ የተለያየ አመለካከት እንደነበር ግልጽ ነው።  ካፒታሊዝም እያደገና ህብረተሰብም መደባዊ አሰላለፉ ግልጽ እየሆነ ሲመጣ  እነዚህ ልዩነቶች ልዩ መልክ በመያዝ ዕውቀት የሚባለው ነገር በተለይም የህብረተሰብንና የኢኮኖሚን፣ እንዲሁም የፖለቲካን ግኑኘንት በሚያንፀባርቅ መልክ እየተረጎሙና እየተጣመመ ሊመጣ ችሏል ማለት ይቻላል። ይህ ጉዳይ በተለይም በኢኮኖሚክስ  ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን ካርል ማርክስና ጓደኛው ፍሪድሪክ ኤንግልስ በተለይም የእንግሊዞችን፣ ከህብረተሰብና ከኃይል አሰላለፍ ጋር ሳይያያዝ የፈለቀውን የክላሲካል ኢኮኖሚክስ በመባል የሚታወቀውን የእነ አዳም ስሚዝን ንድፈ-ሃሳብ ወይም ቲዎሪ  በማሻሻልና አልፎም አልፎም ውድቅ በማድረግ በተጨባጭና በሳይንስ መልክ ካፒታሊዝም በምን መልክና ሎጂክ እንደሚንቀሳቀስና እንደሚተዳደር ለማመልከት በቁ። በእነማርክስ ዕምነትም የካፒታሊዝም ዋናና ተቀዳሚው ዓላማ የህብረተሰብ ጥያቄዎችንና ችግሮችን ለመመለስና ለመፍታት ሳይሆን፣ ትርፍ ማትረፍና ሀብትን በከፍተኛ ደረጃ(Accumulation for accumulation sake or production for production sake) ለማካበት ወይም ለማምረት ብቻ ነው። ስለሆነም ቴክኖሎጂዎችም ሊዳብሩና ለግልጋሎት የሚውሉትና ህብረተሰብአዊ ተቀባይነትም እንዲኖራቸው ማድረግ ከዚህ ስሌት በመነሳት እንጂ አንድ ካፒታሊስት ሰብአዊ ወይም ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት አይደለም። ማርክስ በጭፍን ካፒታሊዝምን ያወገዘ ወይም ደግሞ በዝባዥ ስርዓት ብቻ እንደሆነ በጥላቻ አልጻፈም። የካፒታሊዝምን የስልጣኔ ሚና ወይም ዕድገትን አምጭነትና ህዝብን የሚያስተሳስር ስርዓት መሆኑን አመልክቷል። በተለይም በቴክኖሎጂው ዕድገትና መሻሻል የተነሳ ሰራተኛው እንደድሮው ከሚፈለገው ሰዓት በላይ እንዳይሰራ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። በቴክኖሎጂ ዕድገትና መሻሻል በተወሰነ ሰዓት የበለጠ ማምረት እንደሚቻል አመልክቷል። ይሁንና ሰራተኛው ከተሻሻለው ቴክኖሎጂ ጋር ለመስተካከል በፈጣንና በጥልቀት መስራት እንዳለበት ይህንን በሰፊው ተመራምሯል።  ከዚህም በላይ የካፒታሊዝም ዋናው ዓላማ ትርፍንና ሀብትን ማካበት ቢሆንም የግዴታ የተወሰኑ ኖርሞችን ማሟላት አለበት። በሌላ አነጋገር ፣ ማንኛውም አምራች፣ ካፒታሊስትም ሆነ ነጋዴ ትርፍ ለማትረፍ ሲሉ ብቻ ህብረተሰብን የሚጎዳ መሳሪያም ሆነ ምግብ አያመርቱምም፤ ወይንም ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን በመቀላቀል ገበያ ላይ ወጥቶ እንዲሸጥ አያደርጉም። ማንኛውም ካፒታሊስት ሆነ ነጋዴ በፍጆታ ተጠቃሚው ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ምርታቸውን በተከታታይ እንዲሸጥላቸው የግዴታ የምርታቸውን ጥራት መመርመር አለባቸው። መንግስትና የመንግስት ኢንስቲቱሽኖችም ምግብንና በምርት ክንዋኔ ላይ የሚውሉትን ማሺኖችን በሙሉ የመቆጣጠርና የመመርመር ግዴታ አለባቸው። በገበያ ላይ የሚቀርቡት ምርቶች ተመርምረው ለጤንነት ጠንቅ ከሆኑ ያኔውኑ ከገበያ እንዲወጡ ይደረጋሉ። ሆን ተብለው የተመረቱና ጤንነት ላይ ጠንቅ የሚያመጡ ከሆነ ደግሞ አምራቹ ፈቃዱን ይነጠቃል። ይሁንና እንደዚህ ዐይነት ነገሮች ታይተውም ሆነ ተሰምተው አይታወቁም።

ለማንኛውም በኢኮኖሚክስም ሆነ በሶስዮሎጂና በተለያየ የዕውቀት ዘርፍ ላይ የተደረገውን ርብርቦሽና ከብዙ ምርምር በኋላ ዳብረው የወጡትንና እንደመመሪያ የምንጠቀምባቸውን ዕውቀቶች ለተመለከተ ተመራማሪዎቹና ያዳበሩት ሰዎች እንደ መደብና እንደንቃተ-ህሊና አወቃቀራቸው ከፍተኛ የሞራል ብቃት እንዳላቸው እነገነዘባለን። እንደነ ላይብኒዝና ካንት እንዲሁም ሄገልስና ማርክስ፣ ሌሎችም ጭምር የሞራል ብቃት ባይኖራቸው ኖሮ እንደዚህ ዐይነቶችን ለሰው ልጅ መጠቀሚያ የሚሆነ ዩኒቨርሳል ዕውቀቶችን ባልፈጠሩና እንድንጠቀምባቸው ባላደረጉ ነበር። መመሪያቸው ሀቀኝነትና ለሰው ልጅም ቁም ነገር አስተላልፎ መሄድ እንጂ እንደኛው አገር ምሁራንና ታጋይ ወይም ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ቂም-በቀልን መያዝና መወጣትና አንድ ህብረተሰብ የዝንተ-ዓለሙን በጎሪጥ እየተተያየና አልፎ አልፎም እየተናደፈ እንዲኖር አድርጎ መሄድ አይደለም። በእነዚህ ታላላቅ ምሁራን ዘንድ አንድን ህብረተሰብ ማከረባበትና ፖለቲካን መሸወጃ መሳሪያ ማድረግ፣ ወይም ደግሞ አንዱን ማቅረብና ሌላውን ማራቅ፣ ወይም ደግሞ መጠራጠር የሚባሉ ነገሮች በአስተሳሰባቸው ውስጥ የለም። ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ነገሮች በሙሉ በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር የሚመረመሩና በተግባርም የሚረጋገጡ መሆን አለባቸው። ጭንቅላታቸው በሙሉ ውስጣዊ የሆነ መመሪያ ያለውና በዚህ በዳበረ መመሪያ አማካይነት በመመራት ነበር  ለሰው ልጅ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ፈጥረውና አስተላልፈው ለመሄድ የበቁት። ለዚህም ደግሞ መቶ በመቶ ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል። ዛሬ የምንጠቀምባቸው፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የምንጓዝባቸው፣ በጠቅላላው ሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበሩት ትላንትናና ዛሬ ሳይሆን ቅድመ-ሁኔታዎች በሙሉ ከሶስት ሺህና ከአራት ሺህ ዓመት በፊት የተነጠፉና፣ በየጊዜው ብቅ ባሉና በተገለጸላቸው ምሁራን ወይም አዋቂዎች አማካይነት በዚያው ላይ በመመርኮዝ እየዳበሩና እየተስፋፉ የመጡ ናቸው ማለት ይቻላል። እነዚህ ታላላቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም በተለያየ ዕውቀት የተካኑ ምሁራን ከመጀመሪያውኑ ስራቸው በሙሉ ተንኮል ቢሆንና አገርን መበጥበጥና አጓጉልና ከታሪክና ከህብረተሰብ ልምድ ጋር የማይገናኙ ነገሮችን እየፈጠሩ አንድ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲበጣበጥ የሚያደርጉ ቢሆኑ ኖሮ ምን ዐይነት ዓለም ውስጥ እንኖር ነበር? የሚያሳዝነው ነገር ግን ስንትና ስንት ፈላስፋዎች፣ የሞራልና የስነ-ምግባር አስተማሪዎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎችና የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች፣ እንዲሁም የሶስዮሎጂና የኢኮኖሚክስ ምሁራንን አስተዋፀዖ ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባታችን ነው። ትንሽ ቆም ብለን ዛሬ የምንጠቀምባቸውን ነገሮች በሙሉ ማን ፈጠራቸው፣ እንዴትስ ተፈጠሩ ወይም ተመረቱ ብለን ሳንጠይቅ አገርን ለማፈራረስና ህዝብን ለመጨረስ መነሳታችን ነው። ከዚህም በላይ በየፋብሪካው ተቀጥሮ በመስራት ምርትን የሚያመርተውና እንድንጠቀምባቸው የሚያስችለን፣ በገጠር ውስጥ በእርሻ ተግባር በመሰማራትና ምግብ እያመረተ እንድንመገብ የሚያደርገንን የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ውለታና ታታሪነት ዘንግተን በእልክና በቂም-በቀልነት፣ እንዲሁም በዘመናዊ መሳሪያ በመታጠቅና በመኪና በመንፈላሰስና በስማርት ፎን በመጠቀምና በመደወል ህዝባችንን መቆሚያና መቀመጫ ስናሳጣው የሚያሳፍርም የሚያስዝንም ነው። ይህ ዐይነቱ የግንዛቤ እጦት ዋናው ምክንያት ትግል ብለን ስንጀምር አንዳችም መመሪያና ጠለቅ ያለ ምሁራዊ ብስለት እንደሌለን ነው የሚያረጋግጠው። ዞሮ ዞሮ በፍልስናና በሳይንስ ላይ ያልተመረኮዘ ትግልና፣ አንድን ተጨባጭ ሁኔታና የስነ-ልቦና ጉዳይ በቲዎሪ አማካይነት ሳይመረመርና ሳይተነተን የሚጀመር ትግል የመጨረሻ መጨረሻ አገርን ያፈርሳል፤ አንድን ህዝብ ተሰዳጅ ያደርገዋል፤ ታሪክን እንዳይሰራ ያግደዋል። ህዝቡም ለማኝና ለዘንተ-ዓለም ደሃ ሆኖ እንዲኖር ይፈረድበታል። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በነፃነት ስም የሚነግዱ ታጋዮችና በስለላ ሙያ ሰልጥነው ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን የሚያገለግሉ ምሁራን ነን ባዮች ኢትዮጵያውያን ዓላማቸው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ሌላው  ተጎራባች ህዝብ የስልጣኔ ባለቤት በመሆን እፎይ ብሎ እንዳይኖር  ለማድረግ ነው። አገርን መበጥበትና ህዝብን እረፍት ማሳጣት መነገጃቸው ወይም የቢዝነስ ሞዴላቸው ስለሆነ በዚህ ዐይነቱ እርኩስ ስራቸው ይቀጥሉበታል።

ባጭሩ ስለፖለቲካ ስናስብና እንታገላለንም ብለን ስንነሳ ከፍልስፍና፣ ከህብረተሰብ ሳይንስ፣ ከተለያዩ የኢኮኖሚክስ ዕውቀቶች፣ ማለትም፣ ከመርከንታሊዝም የፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ዕውቀት፣ ከፍዚዮክራቲክስ ወይም የእርሻን ተግባር ዋናው የሀብት ምንጭ አድርጎ ከሚመለከት ዕውቀት፣ ከክላሲካል ኢኮኖሚክስ ወይም እነ አዳም ስሚዝ ካፈለቁትና ካዳበሩት፣ ከማርክሲስት የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ጋር፣ እነ ቬብለንና ሹምፔተር ካዳበሩት ኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስ፣ እንዲሁም ሂስቶሪካል ስኩል ከሚባለው የኢኮኖሚክስ ዕውቀት ጋር፣ እንዲህም ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህም በላይ የአንድን ህብረተሰብ የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ከፍተኛ  ሚና መረዳት ለማንኛውም ፖለቲካ ነኝ ባይ መመሪያው መሆን አለበት። በሌላ ወገን ደግሞ ማንኛችንም ብንሆን በሁሉም ነገር ላይ ቀርቶ እንኳ በአንዱ የዕውቀት ዘርፍ ላይም ቢሆን የተሟላ ዕውቀት ሊኖረን በፍጹም አይችልም። እንደዚህ ብሎ ማሰብም ትልቅ ግብዝነት ነው። ዋናው ቁም ነገር ግን የተወሳሰበ ዕውቀትን አስፈላጊነት መረዳቱ ሲሆን፣ በአንድ ሀብረተሰብ ውስጥ የሚገኙም ሆነ የሚፈጠሩ ችግሮች ሊቀረፉም ሆነ ሊወገዱ የሚችሉት በተንኮልና በጦርነት ሳይሆን በዕውቀት አማካይነት ብቻ እንደሆነ መረዳቱ በራሱ በቂ ነው። ዕውቀት ሳይሆን ተንኮል፣ ሳይንስ ሳይሆን ብጥብጥ፣ ከፍልስፍናዊ አስተሳሰብና አንድን ነገር ከታሪክ ሂደት አንፃር ከመመርመር ይልቅ ቶሎ ብሎ ወደ ግብ ግብ ማምራት የመጨረሻ መጨረሻ አንድን አገር ማፈራረሱ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ መሰረት ጥሎም ለመሄድ አስቸጋሪ እንደሆነ መገንዘቡ የታሪክና የሞራል ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ስለዚህ የተሰራው ስህተትና የታሪክ ወንጀል እንዳለ ሆኖ ወደፊት ለሚነሳውና በፖለቲካ ዓለም ውስጥ እሳተፋለሁ ለሚለው እዚህ ዐይነቱ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት እራሱን እየመላለስ መጠየቅ አለበት። ታሪክን ሊሰራ የሚችልና ህብረተሰብአዊ  ኃላፊነትን ለመወጣት የሞራል ብቃት ያለው መሆኑን ማውጣትና ማውረድ፣ እንዲሁም ከልጅነቱ ጀምሮ ከፍተኛ ዝግጅት ያደረገ መሆን እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል። የአውሮፓን ምሁራንና ፖለቲከኞችን ታሪክ ስንመለከት የምንገነዘበው ነገር የፖለቲካ ትግል የሚጀምሩት ከአስራ አምስት ዐመታቸው ወይም ከዚያ በታች ጀምሮ ነው። አነሳሳቸውም ከብሄረሰብ አንፃር ወይም ደግሞ በግብዝነት ፖለቲከኛ ልሁን ብሎ ሳይሆን የማህበራዊ ጥያቄዎችንና የፍትሃዊነትን ጉዳይ በማንሳት ብቻ ነው። በጥንቱ ዘመን ስልጣኔ የሚባለው ነገር በተለያየ መልክ የሚገለጽ ህብረተሰብአዊ  ፕሮጀክት ሲሆን፣  በሂደት ውስጥ የኃይል አሰላለፍ ሲለወጥና የሞራል መዛባት ሲፈጠር የፍትህ ጉዳይና የማህበራዊ ጥያቄዎች ከፍተኛ  ቦታ ሊሰጣቸው  እንደቻለ መገንዘብ ይቻላል። በተለይም በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ላይ በኢንዱስትሪ ዕድገት እየመነጠቁ በመጡ እንደ ጀርመን በመሳሰሉት አገሮች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማህበራዊ ጥያቄ ጋር መያያዝ እንዳለበትና፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ለኢኮኖሚ ዕድገት ተብሎ ሳይሆን የማህበራዊ ጥያቄዎችንም  ለመፍታትና የሰውን ልጅ ኑሮ ከማቃለል ጋር በማያያዝ  እስከዚያን ጊዜ ድረስ ስለኢኮኖሚክስ የነበረውን ግንዛቤ በአዲስ መልክ እንዲጻፍና እንዲተነተን ተደረገ። ይህም የሚያረጋግጠው በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉትና ከኃይል አሰላለፍና ከፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ዕውቀቶች ዘለዓለማዊ እንዳልሆኑና ዓለም አቀፋዊ መመሪያም ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው። ስለሆነም የህዝባችንን ዕድል እንወስናለን ብለው የሚነሱና ስልጣንም ለመጨበጥ የሚፈልጉ ኃይሎች አንድ ዐይነት የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና ፖሊሲ እንደሌለ ማወቅ አለባቸው።  የአንድ አገር የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ በውጭ ኃይሎች ወይም እራሱን የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ ብሎ በሚጠራው ረቆ የሚቀርብ ሳይሆን በአገሬው መንግስትና በምሁራኑ ብቻ ነው። በተለይም የአንድ አገር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ከማንበብና ከመተንተን አኳያ መነደፍ ያለበት ስልሆነ አንድ የሃርባርድ ወይም የሌላ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ከሩቅ ሆኖ በመጻፍ ይህን  ፖሊሲ  ነው ተስማሚው ብሎ ሊያቀርብና ሊያማክር በፍጹም አይችልም። የአንድ አገር ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሁለ-ገብ ባህርይ  ያለውና፣ የአንድን አገር ችግርም ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችልና አጠቃላዩ ኢኮኖሚም በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የሚችልና ህዝቡን የሚያስተሳስር መሆን አለበት። አንድ ህዝብና ህብረተሰብ ሊተሳሰሩና ሊጠነክሩ የሚችሉት በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ በስራ-ክፍፍል የዳበረ ኢኮኖሚ ሲኖራቸው ብቻ ነው።  ባጭሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ከአጠቃላይ ስልጣኔ ጋር መያያዝና የስነ-ልቦናን ጉዳይ ያካተተ መሆን አለበት።

ፓለቲካ ዕምነትን ወይም ራዕይን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው !                  

በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተካሄደውን የፖለቲካ ትግል ለመረመረ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ገብቶ የሚታገል በሙሉ ከፖለቲካ ዕምነት በመነሳትና እራሱን ከአንዳች ራዕይ ወይም ርዕዮተ-ዓለም ጋር በማገናኘት ብቻ ነበር። ይሁንና ግን የፖለቲካ ትግል ከርዕዮተ-ዓለም ጋር ከመያያዙ በፊት እስከ ኢንዱስትሪ አብዮት ድረስና፣ ካፒታሊዝም አድጎ የሰውን ህይወት ከማዳረሱና ከመደንገጉ በፊት ይደረግ የነበረው የፖለቲካ ትግል ከሰብአዊነት(Humanism) ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የትግል ስትራትጂ የዘመኑ የጊዜ መንፈስ(Zeitgeist= the spirit of the time) ነበር ማለት ይቻላል። ትግሉም የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ማሾል ወይም ማዳብርና አርቆ እንዲያስብ በማድረግ ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ ነበር። ትግሉም ስልጣንን ለመያዝ የሚደረግ ሳይሆን በጊዜው በጎሳ አማካይነት የኋላ ኋላ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ በጠገቡ የገዢ መደቦች የሚነሱ ጠርነቶችን ለማስወገድና ሁለ-ገብ በሆነ መልክ የሚገለጽ ህብረተሰብአዊ  ዕድገትንና ባህላዊ ለውጥን ማምጣት ነበር። ይህ ዐይነቱ የትግል ዘዴ እንደየ ሁኔታዎችና እንደ ህብረተሰብ ውስብስብነት የተለያየ የዕድገት ደረጃዎችን በማለፍ በማወቅም ሆነ ሳይታወቅ ለሚቀጥለው ስርዓተ-ማህበር ሁኔታዎችን አመቻችቶ አልፏል ማለት ይቻላል። የዚህ ዐይነቱ የትግል መሰረትም የፖለቲካ ፍትሃዊነት(Political Justice) ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን፥ ይህ ዐይነቱ የትግል ዘዴ ሁሉንም ነገር ያካተተና ጠቅላላውን የሰውን ልጅ ኑሮና ህይወቱን በሙሉ የሚመለከት ነበር። በዚህ ዐይነቱ የትግል ሂደት ውስጥ ጥበብ ከፍተኛውን ቦታ ሲይዝ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይልና ስራው ጥበባዊ በሆነ መልክ የሚገለጽ መሆን አለበት። በሰብእዊነት ላይ የተመሰረተው የመጀመሪያው ስልጣኔ በሮማውያን አገዛዞች ከፈራረሰ በኋላና ከእነሱ አገዛዝ ማክተም በኋላ የጨለማው አገዛዝ በመስፈን የኋላ ኋላ ፊዩዳሊዝም ለሚባለው ስርዓተ-ማህበር ቦታውን ይለቃል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የተደረገው ትግል ከፊዩዳሊዝም አነሳስ፣ ዕድገትና መዳበር እንዲሁም ከፍጹም ሞናርኪዎች አገዛዝ ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህ ዐይነቱ ትግል አውቆም ሆነ ሳይታወቅ የተለያየ የትግል ደረጃዎችን ያለፈና ለየት ባለ ዕውቀት የተደገፈ ነበር። በገበሬው ላይ ይደረግ የነበረው የብዝበዛ ስርዓትና ገበሬው እንዳለ ነፃነቱን መገፈፉና ካለባላባቱ ፈቃድ ማግባትም ሆነ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድለት የተመለከቱት የተገለጸላቸው ምሁራን ጨለማውንና መንፈስን የሚቆልፈውን ስርዓት መታገል እንዳለባቸው ተገነዘቡ። መሳሪያቸውም በዕውቀት አማካይነት የመንፈስን የበላይነት መቀዳጀትና ስርዓቱን መታገል ነበር። በእነሱ ዕምነትም ዕውነተኛ ነፃነትና ስልጣኔ የሚመጡት በመሳሪያ ትግል ሳይሆን በዕውነተኛና ሁለ-ገብ በሆነ ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነበር። የዳንቴ የአምላኮች ኮሜዲ የሚባለው መጽሀፍ የሚያረጋግጠው ይህንን ሲሆን የመጀመሪያው ሁለ-ገብ የሆነ የትግል መሳሪያና መመሪያ ዕውቀት ነው ብሎ መናገር ይቻላል።  ስለሆነም ትግሉ ሁለ-ገብና በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘና ተጨባጭ ሁኔታዎችንና የስነ-ልቦናን ጉዳይ በማንበብ የተነደፈ ነበር።  በተለይም እንደተፈጥሮ ሳይንስና አርት፣ እንዲሁም በጊዜው የነበሩ ጨለማ ሁኔታዎችን የሚገልጹ ድርሰቶች ሲፈልቁና ሲዳብሩ ፊዩዳላዊውና ዲስፖታዊው አገዛዝ በድሮ መልኩ ሊገዙ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።  ንግድና የዕደ-ጥበብ ሙያ ሲስፋፉና ሲዳብሩ፣ እንዲሁም አዳዲስ የአርኪቴክቸር ህንጻዎች ሲገነቡ የኃይል አሰላልፍ ይለወጣል። አዲስ ብቅ ያለው ህብረተሰብአዊ ኃይል እራሱን በእራሱ ማግኘት ሲችልና የነበረበትን ሁኔታ ሲገነዘብ በተለይም ፖለቲካ በዚህ መልክ መካሄድ እንደሌለበት ይረዳል። ፈላስፋዎችና ሳይንስቲስቶች የነበረውን ዲስፖታዊ አገዛዝ በመጋፈጥ መንግስትና የመንግስት ሚና፣ እንደዚሁም ውስጣዊ ይዘቱ ምን መምሰል እንዳለበትና ተግባሩም ምን እንደሆን ይተነተናሉ። በዚህ መልክ ትግሉ እየተሰፋፋ ሲሄድ ግለሰብአዊ  ነፃነትና ሪፑብሊካዊ አስተዳደር አስፈላጊ መሆናቸው ይሰበካል። አንድ ንጉስና አገዛዝ በአንድ ህዝብ ላይ ዝም ብለው እንዳማይገዙና በህይወቱም ላይ መደንገግ እንደሌለባቸው በግልጽ ይጻፋል። ስለሆነም የአንድ መንግስት ሚና አንድን ህዝብ ጥበባዊ በሆነ መልክ ማስተዳደር ነው። ይህ ዐይነቱ የአስተአሳሰብና የማቴሪያል ለውጥ ቀስ በቀስ ለካፒታሊዝም መጸነስና ማደግ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በተለይም በጊዜው ሚናቸውን የተረዱ ፍጹም ሞናርኪዎች በሁኔታው በመገፋትና በመገደድ ለህብረ-ብሄር ግንባታ የሚያመች ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ለከበርቴው መደብና ለብሄራዊ ስሜት መዳበር መሰረት ይጥላሉ። የከበርቴው መደብ እራሱን የቻለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይል ሆኖ በመውጣት ፍጹማዊ አገዛዝን መጋፈጥ ይጀምራል። በዕዳም ይተበተትባቸዋል። አልፎ አልፎም የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በመግዛት አስተዳደርን ለሱ በሚስማማ መልክ ያዋቅራል። ብቃት ባለው ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር ብቻ ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ ይገባል። ይህ ሁኔታ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተንሰራፍቶ የነበረውንና ለዕድገት እንቅፋት የሆነውን የፊይዳል ስርዓት በመጋፈጥ ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ይወጣል።  ይህ ሁኔታ ለኢንዱስትሪ አብዮት መንገዱን ክፍት ያደርጋል።

በሶስተኛ ደረጃ፣ ከካፒታሊዝም ዕድገትና ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር የተያያዘውን አዲሱን የብዝበዛ ስርዓት መታገልና የሰራተኛውን መደብ ከአሰልቺና ከተደጋጋሚ ስራ፣ እንዲሁም ከብዙ ስዓት ስራ ማላቀቅና ሰው መሆኑን ማስገንዘብ ነበር። በዚህ ዐይነቱ የትግል ሂደት ውስጥ በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከፍተኛውን ቦታ በመያዝና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በመያያዝ ትግሉ ሌላ መልክ ይይዛል።  በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት በመካሄድ ላይና ከተካሄደም በኋላ በጊዜው የተነሱት ምሁራን አስተሳሰባቸውን ጥልቅ በማድረግና በማሾል የህይወትን ትርጉም በመረዳት በተለይም በጊዜው በግልጽ ይታይ የነበረውን ብዝበዛና አሰልቺ ስራ ተገቢ አለመሆኑን በማሳየትና ተቃውሞአቸውን በማሰማት  የሰራተኛው መደብ ኑሮ እንዲሻሻል ትግል ያደርጋሉ። ይህንን ሲያደርጉ በሙሉ ዕምነትና በተግባር የሚያዩትን በቲዎሪ ደረጃ በመመርመርና በመጽሀፍ መልክ በማሳየት ብዝበዛ የሚቀነስበትን ወይም የሚወገድበትን ዘዴ ማሳየት ነበር። ይህንን በሚመለከት በተለያዩ ምሁራን ዘንድ የተለያየ አመለካከት ቢኖርምና እንዴትስ የፖለቲካ ስልጣንን በመቀዳጀት ፍትሃዊ አገዛዝ መመስረት ይቻላል በሚለው ላይ ስምምነት ባይኖርም በሁሉም ዕምነት ግን ጭፍን ብዝበዛና መረን የለቀቀ ጭቆናዊ  አገዛዝ ቦታ እንደሌላቸው ማሳየትና መታገል ነበር። በእነሱ ዕምነትም ጥቂቶች ስልጣናቸውን ተገን አድርገው አንድን ሀዝብ የሚያሰቃዩበት ምንም ምክንያት የለም፤ ማንኛውም ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን አንዱ በሌላው ላይ ፍላጎቱን በመጫን የሚበዘብዘውና የሚያሰቃየው ሳይሆን በእኩልነት የሚታይና የሚከበርም ነው። ስለሆነም አንዱ በአንድ አጋጣሚ በመነሳት ሌላውን አምሳያውን ተፈጥሮአዊ ነፃነቱን በመንጠቅ የሚያሰቃየው መሆን የለበትም። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥም አንድ ህብረተሰብ ሊያድግና ቴክኖሎጂዎችና የስራ-ክፍፍል መዳበር አይችሉም። አንድ ህዝብ የተሟላ ነፃነት ሲኖረው ብቻ ነው ማሰብና መፍጠር የሚችለው። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ለኢንላይተንሜንት ምሁራንም ሆነ ከዚያ በፊት ለነበሩት ታላላቅ ፈላስፋዎች ግልጽ ነበር።

ካፒታሊዝም እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ የወዝ አደሩ መደብ የግዴታ በሙያ ማህበሩ መደራጀት አስፈላጊ እየሆነ መጣ። ትግሉም ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ጥያቄዎች በማለፍ ወደ ፖለቲካ ተሸጋገረ። ቀሰ በቀስም ሶሻሊስታዊ አመለካከት ሲዳብር የግዴታ የወዝ አደሩ መደብ እራሱ ስልጣንን መቀዳጀት አለበት የሚለው አስፈላጊ ጥያቄና አጀንዳ እየሆነ መጣ። ይሁንና ግን የሶሻሊስቶችን ወይም የኮሙኒስቶችን ጥያቄና ግፊት ለማዳከም የማህበራዊ ጥያቄዎች መመለስና ለዚህም ድርድር አስፈላጊ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገባ። ስለሆነም በመጀመሪያ የነበረው ራዲካል የመሰለ አመለካከት በፖለቲካ ኤሊቱ ዘንድ ክፍፍልን በመፍጠር በአንድ በኩል የግዴታ ስልጣንን መንጠቅ ያስፈልጋል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ካፒታሊዝምን በጥገና ለውጥ ማሻሻል ይቻላል በሚሉት ዘንድ ሽኩቻን ፈጠረ። በተለይም የኮሙኒስትንና የሶሻል ዲሞክራቲክን ራዕይ በሚከተሉ መሀከል ክፍፍል በመፈጠር በሃያኛው ክፍለ-ዘመን አፍጦ አግጦ የመጣውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተባብሮ ለመፍታት አስቸጋሪ መሰናክል ተፈጠረ። ይህ ዐይነቱ የወዝ አደሩን ርዕዮተ-ዓለም እንከተላለን በሚሉ ዘንድ የተፈጠረው ክፍፍልና አመለካከት ለቀኝ አክራሪዎችና እንዲያም ሲል ቀስ ቀስ እያለ በዘረኝነት ላይ በመመስረት ሌላና አደገኛ ራዕይ ለሚከተለው ፋሺዝም ተብሎ ለሚጠራው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በር በመክፈት አዲስ ዐይነት የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ሊፈጠርና ህዝቡንም ግራ ሊያጋባው ቻለ። በተለይም የፋሺዝምን አነሳስና ምንጩን ለመረዳት የተለያዩ የፖለቲካ ፈላስፋዎች የተለያየ ቲዎሪ አላቸው። በሌላ ወገን ግን በአብዛኛዎቹ ዘንድ ያለው ስምምነት የፋሺዝም አነሳስ ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በተለይም የከበርቴው ዲሞክራሲና የከበርቴው መደብ በደንብ ባላደገበትና ኢንላይተንሜንት የሚባለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ በጉልህ በማይታወቅበትና እንደምሁራዊ እንቅስቃሴና ኃይል ባልዳበረበት አገር ወይም አገሮች ውስጥ ፋሺዝም ብቅ ማለት እንደቻለና፣ በተለይም ንዑስ-ከበርቴውን ለመያዝ እንደበቃ ወይም የንዑስ ከበርቴው ርዕዮተ-ዓለም እንደሆነ ያስተምራሉ። በተለይም በትንሽ ወይም በተሳሳተ ዕውቀት የተለከፉ ኃይሎችና የህብረተሰብን ህግና  እንዲሁም የልዩ ልዩ ኃይሎችን አስተዋፅዖ ከቁጥር ውስጥ የማያገቡ ለዚህ ዐይነቱ ርዕዮተ-ዓለም ሰለባ በመሆን የተወሰነውን ህዝብ ማኒፑሌት ማድረግ ይችላሉ።

ያም ተባለ ይህ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ትግል ሲጀመርና ሲካሄድ የፖለቲካ ትግል ካለቲዎሪና ካለራዕይ የማይታሰብ እንደሆነ ግልጽ ነው። በፓርቲ ደረጃም የተደራጀውና ይህንን ወይም ያኛውን ርዕዮተ-ዓለም አካሂዳለው ብሎ የሚነሳው አገር ከሚለው ጽንሰ-ሃሳብና አገርን ከማስቀደም ሳይሆን ከቆመለት መደብ አንፃር ብቻ በመነሳት ነው። አገርና ህብረ-ብሄር የሚሉት ፅንሰ-ሃሳቦች የተጠናቀቁ ስለሆነ ወይም ኢኮኖሚው በፀና መሰረት ላይ የተገነባ ስለሆነ በተለይም ለሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎችና ለሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ወይም በጊዜው አረንጓዴ ፓርቲ ወይም የግራ ፓርቲ ተብለው በሚታወቁትና በሚታገሉት ዘንድ የሚነሳው አጀንዳ የአገር ጉዳይ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ፣ የማህበራዊ ጥያቄ፣ የቤት ጉዳይና የኢኮሎጂ ጉዳዮች… ወዘተ. ናቸው። ፓርቲዎችን የሚያሳስባቸውና የሚያጨቃጭቃቸው  እንዴት አድርገው የወደፊቱን የህዝቡን ኑሮ እንደሚያሻሽሉና የሚነሳውንም የፍትሃዊነት ጥያቄ በምን መልክና እንዴትስ መመለስ እንዳለባቸው ነው የሚያሳስባቸው ። በተጨማሪም የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ በተለይም እንደ ጀርመን የመሳሰሉት በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘትና የበላይነትን ለመቀዳጀት በምን በምን ዐይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ማትኮር እንዳለባቸው ነው መንግስታትንና ፓርቲዎችን የሚያስጨንቃቸው። ወደ ውስጥ ፖለቲካቸው ስንመጣ ህገ-መንግስቱን መከላከልና መጠበቅ፣ በተለይም ደግሞ አክራሪ ወይም ፖፑሊስት ፓርቲዎች ቦታ እንዳይኖራቸው ወይም የበላይነትን እንዳይቀዳጁ ማድረግና ዲሞክራቲክ ፖርቲ ነን በሚሉት መሀከል ስምምነትንና መተባበርን መፍጠር ነው። በዚህ ስምምነት መሰረት ጥላቻን የሚሰብክና ሰላም የሚነሳ ነገር የሚያስፋፋ ማንኛውም ገለሰብም ሆነ ድርጅት ቦታ የላቸውም። ይሁንና ግን በዘመነ ግሎባላይዜሽንና በካፒታሊዝም ውስብስብነት የተነሳና፣ በተለይም የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም አይሎ ከወጣና ተቀባይነትም ካገኘ ወዲህ ሁሉም ፓርቲዎች ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ ተገደዋል። ይህ ጉዳይ ከሌሎች ነገሮች ጋር በመደመር ቀኝ ነን ለሚሉ የሚንቀሳቀሱበት መድረክ ሰጥቷቸዋል።  ከሰባኛውና ከሰማኒያኛው ዓመት-ምህረት ጋር ሲወዳደር ከምሁራዊ እንቅስቃሴ ይልቅ አድር-ባይነት አይሎ በመምጣቱ የፖለቲካውን ስፔስ ለመቆጣጠር ለሚፈልጉ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። በተለይም አንዳንድ ፓርቲዎች ግልጽና በድብቅ መልክ ተግባራዊ በሚያደርጉት የተዛነፈና ሀብትን ከደሃው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ሀብታሙ እንዲሸጋሸግ በሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ዝቅተኛ ደሞዝ በሚያገኘው የህብረተሰብ ክፍልና  ከፍተኛ ገቢ በሚያገኘው መሀከል ከፍተኛ የሀብት ልዩነት እየታየ ነው።

በአጠቃላይ  ሲታይ ግን በተለያዩ ፓርቲዎች ዘንድ ያለው ልዩነት በማህበራዊ ጉዳዮችና በኢኮሎጂ ጥያቄዎች  ላይ ሲሆን፣ በተለይም እንደ ሊበራል የመሳሰሉ ፓርቲዎችና እስከስተወሰነም ደረጃ ድረስ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ወይም ኮንሰርቫቲብ ፓርቲዎች ነን የሚሉ አብዛኛውን ነገር ለገበያ ተዋንያን መለቀቅ አለበት በማለት ዝቅተኛ ገቢ በሚያገኘውና ከፍተኛ ገቢ በሚያገኘው መሀከል ከፍተኛ የገቢ ልዩነት እንዲፈጠር ለማድረግ በቅተዋል። በተለይም  ለሀብታሞች የቀረጥ ታሪፍን ዝቅ በማድረግና በቡክ ኪፒንግ ቴክኒክ አማካይነት ከሚያገኙት ትርፍ የተወሰነውን እንደመጠባበቂያ እንዲያከማቹና ሌሎችም ብዙ ቀረጥን ላለመክፈል የሚጠቀሙበት ዘዴ፣ እነዚህ ሁሉ በመንግስት ቢሮክራሲው የሚዘጋጁና በሀብታምና በደሃ መሀከል ያለውን የገቢ ልዩነት እንዲሰፋ የሚያደርጉ ናቸው።  ይህ ሁኔታና የፊናንስ ካፒታል አይሎ መውጣት ሀብታሞች የሚባሉት ከ2-3% የሚቆጠሩት ከ80-90% በመቶ የሚቆጠረውን በገንዘብ የሚተመን ሀብትና መሬትንና ቤቶችን ጨምሮ እንዲቆጣጠሩ አስችሎአቸዋል። አሜሪካን ደግሞ 1% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል 90% የሚሆነውን ሀብት ይቆጣጠራል።  በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም የቤት ኪራይን በሚመለከት በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ የሚኖረው መጠነኛ ገቢ ያለው ህዝብ ከፍተኛ ችግርና ጭንቀት ውስጥ ወድቋል። በርካሽ ወለድ ገንዝብ የሚሰበስቡና የትላልቅ ኩባንያዎችን፣ ማለትም የጉግልን፣ የፌስ ቡክን፣ የማይክሮሶፍትንና የትላልቅ ከበርቴዎችንና ኩባንያዎችን ገንዘብ የሚያስተዳድሩ  ሄጅ ፈንድስ(Hedge Fund) በመባል የሚታወቁ  በመዋዕለ-ነዋይ ስም በማሳበብ ቤቶችን በመግዛትና የቤት ኪራይ በማሰወደድ የትርፍ ትርፍ በማካበት ተራውን ህዝብ ከገበያው እንዲወጣ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የየአገሩ መንግስታትና ፓርቲዎች ይህን ዐይነቱን የሄጅ ፈንዶችንና የትላልቅ ኩባንያዎችን ግፊት ለመቋቋም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት የነበረው የፖሊሲ መሳሪያዎቻቸው በሙሉ ተነጥቀውባቸዋል። በተለይም ኒዎ-ሊበራል የሚባሉ የፊናንስ ካፒታሊዝምን ጥቅም የሚያስጠብቁ ኢኮኖሚስቶች የሚያወጡት ሞዴልና ፖሊሲ እየተወሳሰበ በመምጣቱ መንግስታት ሳይወዱ በግድ ለዚህ ዐይነቱ ልቅ ብዝበዛና የሀብት ሽግሽግ ሜዳውን እንዲለቁ ተገደዋል።  የፊናንስ ካፒታል አይሎ መውጣት በሶስተኛው ዓለም አገሮችም ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረና የጥሬ-ሀብትን እየተቆጣጠረ በመምጣት ላይ ነው። በመዋዕለ-ነዋይ ስም በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሰርጎ በመግባት መሬትንና ጥሬ-ሀብትን በመቆጣጠር በመንግስታትም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ጫና እያደረገና እያጣመመ ነው። ወደፊትም ትላልቅ ህንፃዎችን በመግዛትም ሆነ በመስራት የየአገሩን ህዝብ መኖሪያ ሊያሳጣው የሚችልበት ሁኔታ እየተፈጠረለት ነው። ባጭሩ የፋይናንስ ካፒታል የበላይነትን በመቀዳጀት መንግስታትንና ፓርቲዎችን ሽባ ማድርግ ችሏል ማለት ይቻቻላል።

ይህንን አጠቃላይ ሀተታ ትተን ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ የአገራችን ፖለቲካ በዕውቀትና በራዕይ ላይ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ምሁራዊ መሰረት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ ስልጣንን ለመያዝ ከመፈለግና እንዲሁም ቂም-በቀልነትን መሰረት በማድረግ ቁጭትን ለመውጣት የሚደረግ ግብ ግብ ነው።  በአገራችን ምድር በተለያየ ጊዜ ብቅ ብቅ ያሉትን የፖለቲካን አርማ ይዘው የሚታገሉ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ሁኔታና እንቅስቃሴያቸውን ስንመለከት ትግላቸው በሙሉ በአንዳች ቲዎሪ፣ በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በአብዛኛዎቹ ፓርቲዎችም ሆነ የፖለቲካ ሰዎች ነን በሚሉት ዘንድ ቲዎሪ፣ ፍልስፍናና ሳይንስ ቦታ የላቸውም። በተጨማሪም በተለያየ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና ፖሊሲዎችም ላይ ግልጽ አመለካከት የላቸውም። ከዚህም በላይ ማህበረሰብና ጠንካራ ህብረተሰብ፣ እንዲሁም ባህላዊ እሴት ያለው አገር እንዴት መገንባት እንደሚችልና እንዳለበት በሁሉም ፓርቲዎች ውስጥ ለውይይትና ለክርክር አይቀርብም፤ ወይም ደግሞ ህብረተሰብ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ በግልጽ አይታወቅም። በሁሉም ዘንድ ያለው ግንዛቤ ሁሉንም ነገር ገበያው ይፈታዋል የሚል ሲሆን፣ በተለይም የሰው ልጅ ህይወትና የማህበራዊ ጥያቄዎች ቦታ የላቸውም፤ ወይም ደግሞ በፍጹም አይታወቁም። ከዚህም በላይ የውጭው ኃይል፣ በተለይም ኢምፔሪያሊዝም ተብሎ የሚታወቀው የበላይነትን ማስፈኛ ሚሊታሪያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ተፅዕኖና ከመንግስቱ ጋር በመቆላለፍ ለዕድገት ማነቆ መሆኑን ለውይይት በፍጹም አይቀርብም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በሱ ቁጥጥር ስር ያሉት እንደነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ በአገራችንም ሆነ በተቀሩት ደካማ አገሮች ሰተት ብለው በመግባትና መንግስታትን በማባበልም ሆነ ተፅዕኖ በማሳደር የሚጫወቱትን ሚናና አገርንና እሴትን አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያደርጉትን ተፅዕኖ ማንም ደፍሮና ወደ ውጭ አውጥቶ የሚናገርና ለውይይት የሚያቀርብ የለም። በዚህ ዙሪያ የሚጽፍና የሚናገር ሰው ካለ እንደ እብድ ወይም እንደ አክራሪ ነው የሚቆጠረው። ይህም የሚያረጋግጠው በአገራችን ምድር ክሪቲካል የሆነ የፖለቲካ አመለካከትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን የመመልከትና የመመርመር ልምድ እንዳልዳበረ ነው።

ከዚህ ሀተታ ስንነሳ ካለምንም የቲዎሪ መሰረትና ፍልስፍና እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦችም ሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ነን ባዮች ባለፉት 40 ዓመታት ምሁራዊ ዕድገትና ጥልቀት እንዳይኖር ከፍተኛ መሰናክል ለመሆን በቅተዋል ማለት ይቻላል። ስለሆነም የቲዎሪና የፍልስፍና እንዲሁም ሳይንሳዊ መሰረት ሳይኖረው የሚደረግ ፖለቲካ ነክ ነገር የመጨረሻ መጨረሻ ለአምባገነኖችና ለፋሺሽቶች በሩን ይከፍታል። ሳይንሳዊ ግንዛቤና ምሁራዊ ዕውቀት እንዳይዳብሩ በማድረግ መሰረታዊ የስልጣኔ ጥያቄዎችና የህብረተሰብ ችግሮች መፍትሄ እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆናሉ። ይህንን ነው በፓርቲና በነፃነት ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሲያካሂዱ የነበረውና ወደ ጨለማው ዘመን እንድናመራ ያደረጉን። ስለሆነም ፖለቲካ የሚሉት ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ስልጣኔን የሚያመጣ ሳይሆን ድህነትንና ጦርነትን የሚፈለፍል ሊሆን በቅቷል። ወደ ውስጥ ጠንካራ ህብረተሰብና ማህበረሰብ እንድንመሰርት የሚያስችለን ሳይሆን፣ ባልባሌ ነገር በመጠመድና እርስ በእራሳችን በመሻኮት አገራችንን ለውጭ ኃይሎች አጋልጠን እንድንሰጥ የሚያደርግ የፖለቲካ ግብ ግብ በግልጽ ይታያል።  ፓለቲካው ራስን በራስ ከመቻል ይልቅ የዝንተ-ዓለማችንን ጥገኛ የሚያደርገን ሊሆን በቅቷል። ብሄራዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፍና ኩሩ አገር እንድንመሰርት የሚያደርግ ሳይሆን፥ ተገዥነትንና የወጭ ኃይሎች መጨፈሪያ አገር እንድትሆን የሚያደርግና የሚጋብዝ  የፖለቲካ አካሄድ ነው የዳበረውና እንደ ፈሊጥ የተያዘው። በሌላ አነጋገር፣ በፖለቲካ ስም እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችም ሆነ ግለሰቦች ለምን ዐይነት ህብረተሰብና ኢኮኖሚ እንደሚታገሉ ግልጽ አይደለም። ህልማቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ አይደለም። ስለሆነም ለብዙዎቹ የፖለቲካ ቡድኖች በተለያየ ርዕዮተ-ዓለም መሀከል ያለው ልዩነት ግልጽ አይደለም። በሌላ ወገን ግን ርዕዮተ-ዓለም ወይንም አንድ አቋም በሳይንስና በፍልስፋና ካለተደገፈ በራሱ ለብቻው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለሚታዩ ችግሮችና የችግሮችን መነሻ ምክንያት ለማወቅም ሆነ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት በፍጹም አያስችልም። ከዚህ ስንነሳ በሳይንስና በፍልስፍና ላይ ያልተመሰረተ ርዕዮተ-ዓለም መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ችግሮችንና ጥያቄዎችን ለመፍታት አያስችልም። በጭፍን አስተሳሰብ ላይ የሚመሰረት ርዕዮተ-ዓለም ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የሚያባብስ ሲሆን፣ የጎሳና የሃይማኖት ጥያቄዎች ደግሞ ልዩ አጀንዳ በመሆን ከመሰረታዊው የህዝብ  ፍላጎት ውጭ ልዩ ዐይነት የትግል መሳሪያ በመሆን ከፍተኛ ውዥንብር እንዲፈጠር ይደረጋሉ። በዚህም መሰረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም አጠቃላይ የሆነው የአገር ግንባታ ጉዳይ ቦታ እንዳይኖራቸው ይደረጋል።

ያም ሆነ ይህ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ ወይም ፖለቲካ ያገባኛል ለሚል ሰው የግዴታ አንድ ዐይነት አቋም ወይም ርዕዮተ-ዓለም መኖሩ በጣም ወሳኝ ነው። በመሰረቱ ርዕዮተ-ዓለም የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የሁለት ቃላቶች ድምር ሲሆን፣ አንድን ህብረተሰብ በምን ዐይነት ራዕይ መገንባት ይቻላል እንደማለት ነው። ይሁንና ግን ርዕዮተ-ዓለም የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ከኮሙኒዝም ወይም ከማርክሲዝም ጋር በማምታት አንዳንድ ሰዎች የማይሆን ነገር ያወራሉ። ፅንሰ-ሃሳቡን አጣመው በማቅረብ ነፃነትና የሊበራል አስተሳሰብን እንደሚቀናቀን አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። እነዚህ ሰዎች የማይረዱት ወይም የማይገነዘቡት ነገር ለአንድ ህብረተሰብ መፍትሄው ከገበያ ኢኮኖሚ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም ብሎ መናገር በራሱ ቀኖናዊ አስተሳሰብ ወይም ጭፍን ርዕዮተ-ዓለም መሆኑን ነው። በተለይም የኒዎ-ሊበራልን ርዕዮተ-ዓለም የሚያራምዱ ምሁራን ሁሉን ነገር ወደ ገበያ ኢኮኖሚና ወደ ጠያቂና አቅራቢ በመቀነስ ሰፋ ያለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ እንዳይገነባ ያደርጋሉ። የባህል ጉዳዮች፣ የቆንጆ ቆንጆ ቤቶች አሰራርና የሚያማምሩር ከተማዎች ግንባታና የአንድ ህዝብ አኗኗር ሁኔታ በኢኮኖሚ ስሌታቸው ውስጥ ስለማይገባ  በተለይም እንደኛ ያሉ ምሁራንን ግራ በማጋባት ከፍተኛ የስነ-ልቦና መረበሽና የሞራል ውድቀት እንዲከሰት ለማድረግ በቅተዋል። ለማንኛውም አንድ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ  ስለ አንድ ህብረተሰብና  አገር ጠበቃ ነኝ ብሎ የሚንቀሳቀስ ከሆነ አስተሳሰቡና ዕምነቱ በአንዳች የርዕዮተ-ዓለም አመለካከት ዙሪያ መሽከርከር አለበት። በሚያምንበትም ርዕዮተ-ዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎችን እንዴት እንደሚፈታ ማመልከት አለበት።

ሌላው በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር የኢኮኖሚው አወቃቀር አሁንም በአብዛኛው ጎኑ ከእጅ ወደ አፍና የሆነና በችርቻሮ ደረጃ የሚካሄድ የንግድ እንቅስቃሴና ኢንፎርማል ሴክተር የሚባለው የህብረተሰቡን የመኖር ሁኔታ የሚደነግጉ በመሆናቸው አሰተሳሰባችንም በዚህ ዐይነቱ በቀጨጨ መልክ በሚካሄድ የተዘበራረቀ ኢኮኖሚና የችርቻሮ ንግድ አኳያ የሚሽከረከር ነው። በሌላ አነጋገር፣  በአገራችን ምድር ስርዓት-ያለው የሰራ-ክፍፍል ያልዳበረ በመሆኑና ያሉትም ከተማዎች የመንደር ባህርይ ስላላቸው ይህ ዐይነቱ ተጨባጭ ሁኔታ አስተሳሰባችንን በመያዝ ለየት ባለ መልክ ልናስብና አንዳች ዐይነት ርዕዮተ-ዓለምና ሰፋ ያለ ምሁራዊ አስተሳሰብ ለማዳበር በፍጹም አልቻልንም። ስለሆነም በአገራችን ምድር ሰብአዊነት(Humanism)፣ የሊበራል አስተሳሰብ፣ የግራ አስተሳሰብ ወይም ኮሙኒስታዊ ርዕዮተ-ዓለምና ሌሎች በካፒታሊስት ስርዓተ-ማህበር ውስጥ የሚታዩና ግለሰቦች እንደዝንባሌያቸውና ዕምነታቸው ተሰባስበው የፖለቲካና የሶሻል አጀንዳ የሚነድፉበት ሰፋ ያለ መድረክ ስለሌለና፣ ዲሞክራሲያዊ ውይይትም ስለማይካሄድ ሁሉም በጭፍን የሚመራ ነው የሚመስለው። በተለይም አንድ ድርጀት ወይም ፓርቲ ነኝ የሚል በምርጫም ሆነ በአንዳች ምክንያት ስልጣን ላይ ቢወጣ የህዝባችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች ለመፍታት አይችልም። እንደምናየውና የዛሬው የአገራችን አገዛዝም እንደሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲውን የውጭ ኃይሎች የሚያረቁለትና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ምክር በመረዳት ሳይወድ በግድ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት ባለው ችግር ላይ ሌላ ችግር በመደረብ ህብረተሰቡ ግራ እንዲጋባ ያደርጋል ማለት ነው።

ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ስንነሳ ካለ ዕምነትና ካለመመሪያ የሚካሄድ ፖለቲካ አንድን ህብረተሰብ አቅጣጫውን እንዲስት ያደርገዋል። እንደሚታወቀው ማንኛውም ነገር መመሪያ ያስፈልገዋል። እንደዚሁም አንድ አገርና ህብረተሰብ መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠንና በዚህች ዓለምም ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ስለሚኖሩ በተለይም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ለህይወታቸው መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ህብረተሰብና አገር ወይም ህዝብ የውጭ ኃይሎች ብልሹ ባህል ማራገፊያና መጫወቻዎች እንዳይሆኑ ከተፈለገና ለሚቀጥለውም ትውልድ በሰላም እንዲሸጋገር  የግዴታ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅትና ፓለቲካ ያገባኛል የሚል ግለሰብ በተወሰነ መመሪያና ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ መሽከርከርና ሃሳቡን በጽሁፍ መግለጽና ማስተማር አለበት። እስካሁን እንደሚደረገው ትግል ወደፊት እንቀጥላለን የምንል ከሆነ የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች በሁለት መቶና ሶስት መቶ ዓመትም ሊፈቱ የማይችሉ ይሆናሉ።

ፖለቲካና ሞራል!

በአገራችን ምድር በቤተክርስቲያን አካባቢ ስለግብረገብነትና ስነ-ምግባር የሚሰበክ ቢሆንም በፖለቲካ ተዋንያኖች ዘንድ ፖለቲካ የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብና ዋናው ተግባሩ በግልጽ የማይታወቀውን ያህል ሞራል እራሱም ተገቢውን ቦታ የያዘና ለውይይትም የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በሌላ ወገን  የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከዛሬ ሃምሳ ዐመት በፊት ሲጀመር በጊዜው በአንዳንድ የተማሪው እስንቅስቃሴ መሪዎች ፖለቲካና ሞራል አንድ ላይ የሚሄዱ እንዳልሆነ ተጽፎ በጊዜው በተማሪው ልሳን ታጠቅ ወይም ትግላችን  በሚባለው መጽሄት ላይ የኋላ ኋላ ያነበብኩኝ ይመስለኛል። ኋላም  በጦቢያ መጽሄት ላይ ይህንን ዐይነቱን ፖለቲካና ሞራል አንድ ላይ ሊሄዱ አይችሉም የሚለውን አባባል በጊዜው የመጽሄቱ አዘጋጅ  በሆነው ሰው ተጽፎ ለማንበብ በቅቻለሁ። ይሁንና ግን የተማሪው እንስቃሴ መሪ የነበረውና ፖለቲካና ሞራል ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም ብሎ የጻፈው ግለሰብ በዚያን ጊዜ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ለመሬት ላራሹና ለዲሞክራሲ ሲታገሉ የተዘነጋው ነገር ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ጥያቄዎች ባሻገርም የመሬት ላራሹና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች የግዴታ ከሞራል ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ነው። በጊዜው የጭሰኛው መበዝበዝና አስከፊ የሆነው የኑሮ ሁኔታና እየደጋገመ ይከሰት የነበረው ረሃብና በከተሞች ውስጥም የተስፋፋው ድህነት ሳላሳሰባቸው ነው የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች የመሬት ላራሹንና የዲሞክራሲን ጥያቄ አንግበው መታገል የጀመሩት። ከዚህ ስንነሳ የግዴታ ፖለቲካና ሞራል የሚያያዙ እንጂ አንዱ ከሌላው ተነጥሎ የሚታይ ወይም ግንዛቤ ውስጥ የሚገባ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ፖለቲካንና ሞራልን ነጥለን የምናይና፣ ፖለቲካዊ ድርጊትን በሞራላዊ ሚዛን መመዘን ካልቻልን በአብዮቱ ዘመን እንደታየውና፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት 28 ዐመታት እንደተገነዘብነው ፖለቲካ የሚባለው ግዙፍ ነገር የዱርዬዎችና የቂም-በቀለኞች መጫወቻ ይሆናል ማለት ነው። መጽሀፍ ቅዱሱ እንደሚለው በራስህ ላይ ሊደርስብህ የማትፈልገውን ነገር ለሌላው አትመኝ የሚለው አነጋገርና፣ ኢማኑኤል ካንት ደግሞ ለራስህ ጥሩ ነገር የምትመኝ ከሆነ ይህንን ምኞትህን ለሌላውም እንዲደርሰው ማድረግ አለብህ የሚለው ሞራላዊ ትምህርት የግዴታ ከፖለቲካ ጋር መያያዝና ለመሪዎችም እንደመመሪያ መሆን አለበት።

ለማንኛውም በሶክራተስና በፕላቶን እንዲሁም በታላላቅ የሬናሳንስ ሰዎች ትክክለኛ ግንዛቤ ፖለቲካና ሞራል አንድ ላይ የተያያዙ ሲሆኑ፣ በየኢፖኩ ይታዩ  ከነበሩ አወዛጋቢ የፖለቲካ ሁኔታዎችና ቅጥ ያጣ ብዝበዛና ጦርነት በመነሳት የተነደፉ መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። ስለሆነም ነው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍትሃዊነት መኖርና በፖሊሲ ደረጃም መረቀቅና በፓርቲዎች አስተሳሰብ ጭንቅላትም ውስጥ እንዲቀረጹ በማድረግ ትግል የሚደረገው። በአጭሩ በአውሮፓ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ  በጊዜው የነበሩ ፈላስፋዎች ስለፖለቲካ ነፃነትና እኩልነት ሲታገሉ፣ ይህም ማለት ጭቆናን ማስወገድና ፍትሃዊ የሆነን ስርዓትም ማስፈር ነው። ይህ በራሱ ደግሞ ለላ ነገር ሳይሆን የሞራል ጥያቄ ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ ከአርባ ዐመት በላይ የፈጀውን እልክ አስጨራሽና አገር አውዳሚ የሆነውን የህዝባችንን ዕልቂት ስንመለከት የነፃነትንና የዲሞክራሲን አርማ አንግበው የተነሱና ትግል የጀመሩ ጭንቅላታቸው ውስጥ የቀረጹትና እንደመመሪያ የሚሆናቸው የሞራልና የስነ-ምግባር ጉዳይ አንዳችም እንደሌለ እንገነዘባለን። ስለሆነም የየድርጅቶቹ መሪዎች ጠላታችን ነው ብለው ባነጣጠሩት ላይ ብቻ ሳይሆን ትንሽ ጥያቄ ያነሳውንና የትግሉ አካሄድና ዓላማ ያላስደሰታቸውን በሙሉ ነው በግፍ ያጨዱት። በተለይም የነጻነት አርማን ይዘው ሲታገሉ የነበሩ የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች ስልጣን ከያዙ በኋላም በዚያው በግፍ ድርጊታቸው ለመግፋት የተገደዱት ከመጀመሪያውኑ ሞራል የሚባለውን ነገር ከጭንቅላታቸው ውስጥ አሽቀንጥረው በመጣላቸው ነው። አሊያም ጭንቅላታቸውንና ድርጊታቸውን የሚቆጣጠር አንዳች ነገር የለም ማለት ነው። በመሆኑም ከኤርትራውም ሆነ ከወያኔው ትግልና ውጤት የምንረዳው እነዚህ ኃይሎች ለህዝባቸው ነፃነትንና ዲሞክራሲን፣ እንዲሁም ብልጽግናን ለማጎናጸፍ እንዳልቻሉ ነው። ለዚህ ምክንያት ደግሞ ቀደም ብለው ምሁራዊ ዝግጅት አለማድረጋቸውና ጭንቅላታቸው በክርክርና በትችታዊ አስተሳሰብ አለመታነጹ ነው። ከተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች ጋር ባለመተዋወቃቸውና በመሀከላቸው ወይም በውስጣቸው ዲሞክራሲያዊ ውይይት እንዲካሄድና የተለያየ ሃሳብ እንዲዳብርና የመጨረሻ መጨረሻ ለአገር ግንባታ የሚያመች አሰተሳሰብ ተጨምቆ እንዳይወጣ ለማድረግ በቅተዋል።  የፖለቲካ ክርክርና ጥናት በሌለበት ቦታ ደግሞ አንድ ድርጅት ወደ ማፊያነትና ወደ አምባገነንነት እንደሚለወጥ የወያኔና የሻቢያ ታሪክ ያረጋግጣሉ። በሽታውም እነሱን አልፎ ሌላውን በማዳረስ የፖለቲካ ሁኔታው ቢለውጥም እንኳ የተበላሸውን ፖለቲካና በውንብድና መንፈስ የተመረዘውን የህብረተሰብ ክፍል ማከምና ማስተካከል ያስቸግራል።

ወደ አብዮቱ ዘመን ስንመጣ አብዮቱ በአጀማመሩ ጥሩ የሆነውን ያህል ሂደቱ እንዲሰናከል ያደረጉና እራሳቸውም ለመሬት ላራሹ ይታገሉት የነበሩ የአንዳንድ ድርጅት መሪዎች በከተማው ውስጥ የትጥቅ ትግል ሲጀምሩና አንዳንድ ግለሰቦችን ሲገድሉ ይህ ዐይነቱ ድርጊት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመገንዘብና ጥያቄም ለማቀረብ የሚችሉ እንዳልነበሩ መገንዘብ ይቻላል። በሌላ ውገን ግን በጊዜው እነዚህ መሪዎች ተሳክቶላቸው ስልጣንን ለመያዝ ቢችሉ  ኖሮ ምን ዐይነት የፖለቲካ ስርዓት መመስረት ይችሉ ነበር? በእርግጥስ ዲሞክራሲያዊ ነፃነትን በማወጅና ሁሉንም ኃይሎች በማስተባበር ህዝባችን አገር በመገንባት ላይ እንዲረባረብ ማድረግ ይችሉ ነበር ወይ? በፍጹም አይችሉም። እነዚህ ኃይሎች የግዴታ ፋሺሽታዊ ስርዓትን ይመሰርቱና ይቃወማቸው የነበረውን ኃይል በሙሉ ያጭዱ ነበር። ስልጣን ሳይጨበጡ ያየነውም ይህንን ሀቅ ነው። ከዚህ ስንነሳ በመኢሶንና በኢህአፓ መሀከል የተፈጠረውና ከምሁራዊና ከሳይንሳዊ ክርክር ይልቅ ጠበንጃን የችግር መፍቻ ማድረግ በመሰረቱ የአገራችን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ውጤት ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል። ሁለቱም ድርጅቶች ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር በመጣ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ትምህርትና  ክርከር የታነፁ ሳይሆኑ የፊዩዳሊዝምና የፔሪፌሪ ካፒታሊዝም ወይም ደግሞ የአሜሪካን ሶስይሎጆስቶች  ዘመናዊነት(Modernization) ብለው በሚጠሩት ለሁለ-ገብ ዕድገትና ለመሰረታዊ ለውጥ በማያመች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የታነጹ ናቸው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የተኮላሸ ዕድገትና በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች እንደምናየው አርቆ-አሳቢነት ሳይሆን አመጽንና የላይ ላዩን መጋለብ የሚያስተምር የዘመናዊነት ፖሊሲ  የንዑስ ከበርቴውን መንፈስ በመያዝ የግዴታ እንደዚያ ዐይነት የእርስ በእርስ መተላለቅና አገርን ማፍረስ ተቻለ። ይህ ሲባል ግን በጊዜው በተማሪው ማህበር ውስጥ አርቆ-አሳቢ ኃይል አልነበረም ማለት አይደለም። ብሄራዊ አጀንዳን በማስቀደም በሚያስማሙ ነገሮች ላይ ለመስራት ሙከራ አልተደረገም ማለት አይደለም። ይሁንና ግን አንድ ጊዜ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ፣ በተለይም ሲአይኤ አብዮቱ የግዴታ መክሽፍ አለበት ብሎ ቆርጦ በመነሳቱ የውስጥ ኃይሎችን በማስታጠቅ የደርግ አገዛዝ  እራሱን እንዳይቆጣጠር ለማድረግ በቃ።  ከውስጥና ከውጭ የተወጠረው የሚሊታሪው አገዛዝ የነበረው አማራጭ ከውስጥም ሆነ ከአካባቢው የተሰነዘረበትን ጥቃት ለመመለስ በጅምላ መጨፍጨፍ ነበረበት። የመጨረሻ መጨረሻም ሲያስተምሩትና ሲመክሩት የነበሩትን በሙሉ ካለምንም ርህራሄ እየገደለ ጉድጓድ ውስጥ በጅምላ ጣላቸው።  የሚያስገርመው ነገር በጊዜው የተደረገው መጨፋጨፍ የማርክሲዝምን ሌኒንዝም አርማ አንግበውና ተራማጅ ነን ብለው ራሳቸውን በሚጠሩ መሀከል የተካሄደ አርቆ-አስተዋይነት የጎደለው መበላላት ነበር።  በአንፃሩ በቻይና የጦር ትግል ሲጀመር አድሃሪ የነበረውን የኮሚንታግን አስተዳደር ለመጣልና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተደረገ ሲሆን፣ በመሃከላቸው ይካሄድ የነበረው የጦር ትግል ለጊዜው በመቋረጥና ሁለቱም ኃይሎች ትግላቸውን በወራሪው በጃፓን ጦር ላይ በማነጣጠር የጃፓንን ወራሪ ኃይል ለማባረር በቅተዋል። እነ ማኦሴቱንግ ከዚያ በኋላ በኮሚንታግ ጦር ላይ በመነሳት ከታይዋን በስተቀር ጠቅላላውን ቻይናን ለመቆጣጠርና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ችለዋል። ይህም ማለት ቻይና ውስጥ የተካሄደው ጦርነት በአድሃሪና በተራማጅ ወይም ለውጥን በሚፈልገው ኃይል ዘንድ ሲሆን፣ አገራችን ግን በዲሞክራሲና በነፃነት ስም ወይም ተራማጆች ነን ብለው በሚምሉና በሚገዘቱ መሀከል ነበር።

ለማንኛውም በአብዮቱ ወቅት በአገራችን በከተማም ሆነ በገጠር ውስጥ በነፃነት ስም ጦርነት ሲካሄድ እዚያው በዚያው ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያመች እርምጃዎችም ተግባራዊ እየሆኑና እየተካሄዱም ነበር። እንደመሬት ላራሹን የመሳሰሉትና ሌሎችም ለጥገናዊም ሆነ ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያመቹ፣  በተለይም እንደ ባንክና መድህን የመሳሰሉት ዘርፎችና ኢንዱስትሪዎችን በመንግስት ቁጥጥር ስር ማድረግና ህዝቡም በየፊናው እንዲደራጅ ማድረግ… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ እርምጃዎች ሁሉንም ኃይሎች ሊያሰባስቡ የሚችሉና በጊዜው ሁሉም ኃይሎች በአገር ግንባታ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ ነበር። ምሁራዊ ብስለት የጎደላቸውና ምንም ዐይነት ሞራል በጭንቅላታቸው ውስጥ ያልተቀረጸ ኃይሎች ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አጠቃላይ ጦርነት በመክፈት ሁሉም ኃይሎች እልክ ውስጥ ተጋቡ። ከዚህ ስንነሳ አብዮት በተካሄደባቸው ወይም በመካሄድ ላይ ባለበት አገር የውስጥ ኃይሎች አብዮታዊ ለውጥን በመቃወም እንደዚህ ዐይነት አጠቃላይ ጦርነት ያወጁበት አገር በዓለም ታሪክ ውስጥ ተፈልጎ አይገኝም። የእርስ በእርስ መበላላት ችሎታ ያላቸውና አገርን አፍራሽ ድርጊት የሚፈጽሙ እንደኛ አገር ያሉ ምሁራን ብቻ ናቸው።

ነገሩን መቋጠሪያ ለማሲያዝ አንድ ድርጅትም ሆነ የፖለቲካ ነገር ያገባኛል የሚል ግለሰብ በፖለቲካ ውስጥ ሲገባ ብዙ ማውጣትና ማውረድ ያለበት ጉዳይ አለ። በመጀመሪያ የራሱን ዕድል ሳይሆን የብዙ ሚሊዮኖች ህዝብንና የተከታታዩን ትውልድ ዕድልና ሁኔታ ስለሚነካና ስለሚወስን በቂ ዝግጅትና ፖለቲካዊ ዕምነትና የሞራል ብቃት ይኑረው አይኑረው እራሱን እየመላለሰ መጠየቅ አለበት። ታሪክን ለመስራት የሚችልና፣ ሌላውንም ለማስተባበርና በጋራ ለመስራት የሚችል መሆን አለበት። ፖለቲካን የራሱ ሀብት አድርጎ የማይቆጥርና ተከታታይና ብሩህ የሆነ አዕምሮ ያለው አዳዲስ ትውልድና ደቀ-መዝሙር ለማፍራት የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። አንድ ዐይነት የህብረተሰብ ሞዴል ከመምረጥ ይልቅ የየአገሮችን ልምድ በመውሰድና ረጅም ጊዜ በማጥናት አንድ አገር እንዴት አድርጎ በጠንካራ መሰረት ላይ እንደሚገነባ ትምህርት መቅሰም አለበት። በጭፍን አስተሳሰብ መመራት ሳይሆን ለውይይትና ለትችት፣ እንዲሁም ለክርክር ዝግጁ መሆን አለበት። ሌላውም ከእሱ የተሻለ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚችልና አማራጫ ፖሊሲንም ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት። ይህ ዞሮ ዞሮ የሞራል ብቃትነትንና ጠለቅ ያለ ምሁራዊ ብስለትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ሁሉ ሳይደረግ ዝም ብሎ በጭፍንና በግብዝነት ፖለቲካ ውስጥ ሰተት ብሎ መግባት የአንድን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የሶስትና የአራት ትውልድንና ከዚያም በበላይ የሆንነ የህብረተሰብ ዕድል ያበላሻል።

 የዛሬው እርስ በእርሱ የሚቃረን ፖለቲካ!  

የዛሬ ዓመት አብዛኛዎቻችን መጣ በሚባለው ለውጥ ፈንድቀንና ተደስተን ነበር። አንዳንዶቻችንም ስልጣን የምናገኝ መስሎን እንደ አቅሚቲ ጊዜውን መጠቀም አለብን ብለን ወዲህና ወዲያ ተሯርጠናል። የዛሬ አንድ ዐመት ተኩል ዶ/ር አቢይ ስልጣንን ሲረከቡ አገራችንን ከሰመጠችበት የፖለቲካ ማጥ አውጥቶ ወደ አዲስ የስልጣኔ መንገድ የሚያራምዳት የተገለጸለትና ከእግዚአብሄር የተላከ ልዩ ሰው ወይም ሜሲያስ ያገኝን መስሎን ነበር። እሳቸው ስልጣኑን ከጨበጡ በኋላ 28 ዐመት ያህልና ከዚያ በፊት የተቦካውንና የተተራመሰውን አገር አፍራሽ ፖለቲካ ግንዛቤ ውስጥ በፍጹም አላስገባንም። አንድ ፈገግና ሳቅ የሚል ሰው፣ እንዲሁም ፍቅርንና መደመርን የሚሰብክ ግለሰብ ስልጣንን ስለጨበጠ ብቻ የአገራችን የተደራረቡ ችግሮችና የፖለቲካ ትርምስ ከመቅጽበት የሚፈቱ መስሎን ነበር። በዚህ ዐይነቱ አመለካከታችንና አስተሳሰባችን ታላላቅ ፈላስፋዎች ያስተማሩንን ነገር ሁሉ ዘንግተን ነበር። አንድን ነገር በተናጠል ወሰደህ ፍርድ መስጠትና አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ሳይሆን ጠቅላላውንና እርስ በእርሱ የተሳሰረውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባትና በመመርመር ብቻ አንድ ውሳኔ ላይ ድረስ የሚለውን ትክክለኛውንና ሳይንሳዊውን አባባል እረስተነው ነበር።

ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከያዙ በኋላ እኛም ሆነ የውጭ አገር ጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶች በሁኔታው ተደንቀን ነበር።  በተለይም ታላቁ አባታችን አሜሪካ በአገራችን ምድር „ሰለሚካሄደው ለውጥና“  ስለ ዶ/ር አቢይ ያላቸውን አድናቆት አብስረውልናል። ከዶ/ር አቢይም ጎን በመቆም „ለውጡ እንዲጠናቀቅ“  ዕርዳታ እንደሚያደርጉ ቃል ኪዳን ገብተዋል። የሚገርመው ነገር የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እነ አቶ መልስ ዜናዊ ስልጣን ሲይዙ እንደዚሁ ከፀረ-ለውጡ ጎን ቆመው ነበር። በዚያን ጊዜ  አብዮቱ እንዲከሽፍና ፀረ-ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ ያልሆኑ ኃይሎች ስልጣን ላይ እንዲወጡ ያላደረጉት ሙከራ አለነበረም። በእርግጥም ተሳክቶላቸዋል።  በስልጣን ላይ ያሉትም የአገራችን መሪዎች „ዓለምን ያስደመመ ወይም ያስገረመ ለውጥ“  ነው በማለት በድርጊታቸው ደስተኛ ሆነዋል፤ ኮርተዋልም። ለውጥ ማለት እንደዚህ ነው ብለው ነግረውናል። ይህንን „የመሰለ ለውጥ እንዳይቀለበስ ሌት ተቀን መስራት አለብን“ ብለው አረጋግጥለውናል። ጋዜጠኞችም ሆነ ከውጭ ተግበስብሶ የገባው ተቃዋሚ ነኝ ባይና ሌሎች በውጭ አገር ሚዲያ ውስጥ ሲሰሩና ወያኔን ሲታገሉ የነበሩ በለውጡ በመደሰት ስለለውጡ ዕምርታነት ብዙ አውርተውልናል። በጣም የሚያስገርም ነገር።

የለውጥን ጉዳይ በሚመለከት እ.አ.አ በሰኔ 11፣ 2019 „ግራ የሚያጋባ ሁኔታ“ በሚለው አርዕስት ስር በጻፍኩትና ባሰራጨሁት ሀተታ ለማብራራት ሞክሬአለሁ። የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታትና ለጊዜው የሚዲያ ነፃነት ከመስጠት በስተቀር ለኢትዮጵያ ህዝብ ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ ተስፋ የሚያስጨብጠውና በጋራ አገሩን ለመገንባት የሚያስችል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተነድፎ ተግባራዊ ሲሆን አይታይም። በዚያው ጹሁፌ ላይና አሁን ደግሞ በቅርብ ባወጣሁት ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በተለይም ጨቋኙና ህዝብን የሚያሰቃየው የመንግስት የመጨቆኛ መሳሪያ እንዳልተነካና፣ እንዲያውም ይባስ ብሎ በመንቀሳቀስና የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ወደድሮው ሁኔታ እንደተመለሰ እንመለከታለን። አንድ ሰሞን ትችትን የሚቀበሉና የሰውንም እሮሮ የሚሰሙ የሚመስሉ የ110 ሚሊዮን ህዝብ መሪ ጠ/ሚኒስተር ጆሮ ዳባ በማለትና አይተው እንዳላዩ በመምሰል ወደ ውስጥ ከማትኮርና አገሪቱን ከማረጋጋት ይልቅ ወደ ውጭ ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ ይመስላል። የዚህ ሁሉ ችግር ከየት የመነጨ ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ በሚለው ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ዶ/ር አቢይም ሆኑ በአጠቃላይ ሲታይ ቲም ለማ የሚባለው ቡድን የረጅም ጊዜ የዲሞክራሲና የምሁራዊ ክርክርና ውይይት ውጤት አይደሉም። ዛሬ ካሉበት „ድርጅት“ ውጭ የመጡና ወይም ደግሞ ከውስጥ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ በመታገል ማንነታቸውን ያሳዩና ያረጋገጡልን ሳይሆን 27 ዐመት ያህል አገራችንን ሲበዘብዝና ሲያዝበዘብዝ፣ እንዲሁም እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፣ በተጨማሪም ልጆቻችን የሚሆኑትን በግፍ ሲገድልና አገርን ሲያተራምስ ከቆየ አገዛዝ አብራክ የተፈጠሩ ናቸው። በወያኔ 27 ዐመት የአገዛዝ ዘመን እነ ዶ/ር አቢይም ሆኑ ሌሎች የኢህአዴግ አባሎችና ፓርሊያሜንት ውስጥ የተቀመጡት በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እንደማይካሄድና አገር ይተራመስ እንዳልነበር ዝም ብለው የሚያዩ ነበሩ። በሌላ አነጋገር፣ ከነገሩ ጋር የተለማመዱና የወያኔን ግፍ አገዛዝና አገር መበዝበዝና ማስበዝበዝ እንደ ኖርማል ድርጊት አድርገው የተቀበሉ ናቸው። በሶሻል ሳይንሱ ሶሻላይዝድ መሆን ሲባል፣ ከሳይኮሎጂ አንፃር ደግሞ ጭፍጨፋና ማሰር፣ እንዲሁም መግደል ሲደጋገም በአንድ አገዛዝ ውስጥ ያለ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሆኖ የሚመለከተውም ከነገሩ ጋር እየተለማመደ በመሄድ ከቁም ነገር ውስጥ የማያገባበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነው። ከዚህ ስንነሳ የወያኔ አሰቃቂ ድርጊት በግልጽ ታይቶና በፊልምም ተቀድቶ ድርጊቱን የፈጸሙት እንደ ጀግኖች በመቆጠር ሽር-ጉድ ሲባልላቸውና ሲሳቅላቸው ስንመለከት የፖለቲከኞቻችን ጭንቅላት የቱን ያህል የደነደነና ከርህራሄ እየራቀ እንደመጣ ነው የምንገነዘበው።

ለማንኛውም አንድ ለውጥን አመጣለሁ ወይም አምጥቻለሁ የሚል አገዛዝ የለውጥ ኃይል ሆኖ ሊቆጠር የሚችለው በተለይም የመንግስት መኪናን ተገን በማድረግ በህዝብ ላይ ጭፍጨፋን ባካሄዱና አገርን ባተረማመሱ ላይ የሚወስደው የማያወላዳ እርምጃ ነው። እንደሚታወቀው ህውሃት በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን  ብቻ ሳይሆን የገደለው አገሪቱን እንዳለ የገደለና በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንድትኖር በቋንቋ ላይ የተመሰረተ „የጎሳ ፌዴራሊዝም“ የሚሉትን ፈሊጥ ተግባራዊ ያደረገ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ዘመን የነበረውንና በደርግ አገዛዝ ዘመን የተሻሻለውን የክፍለ-ሀገራት አስተዳደር አወቃቀር በመበወዝና አዲስ ማንነት እንዲፈጠር በማድረግ አንድ ህዝብ ተስማምቶና ተባብሮ አገሩን እንዳይገነባ ከፍተኛ መሰናክል የፈጠረ የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ ያሟላ ማፊያዊ ድርጅት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የህውሃት አገዛዝ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በሚባለው በመታገዝ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ የሀብት ዘረፋ ያደረገና፣ አገሪቱ በዕዳ እንድትተበተብና የውጭ ንግድ ሚዛኗም በከፍተኛ ደረጃ እንዲናጋ ያደረገ ነው። በዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ አማካይነትም በደሃና በሀብታም መሀከል ያለው ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን አዲስና ከአገራችን የኢኮኖሚና የባህል ሁኔታ ጋር ሊጓዝ የማይችል የፍጆታ አጠቃቀም እንዲገባና የተወሰነው የህበረተሰብ ክፍልም እንዲለምደው በማድረግ የብልግናና የሞራል ውድቀት እንዲስፋፋ ያደረገ ነው። ከዚህም ባሻገር፣ አገሪቱ የቆሻሻ መጣያ እንድትሆን ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ወጣቱ ሞራሉ እንዲከሰከስ የጨአት መቃምና ዕፅ እንዲስፋፋ ያደረገ ነው። በተጨማሪም  ገብረ-ሰዶማዊነት እንዲስፋፋ በማድረግ በአጠቃላይ ሲታይ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀት እንዲከሰትና አገራችንንም ለውጭ የስለላ ኃይሎች አጋልጦ የሰጠ ነው። በአጭሩ የወያኔ አገዛዝ አንድ መንግስት ማድረግ የሚገባውን አገርን በስነ-ስርዓት መገንባትና ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ያደረገ ሳይሆን በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ወንጀል የሰራና  መንፈሱም ከጥፋትና ከተንኮል በስተቀር ምንም ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም የሌለው ነው። ምንም ዐይነት ምሁራዊ መሰረትና ዕውቀት የሌለው በመሆኑ አገራችንን የውጭ አገር ፖሊሲዎችና የተበላሹ ቤት አሰራሮች መሞከሪያ ያደረገና ህዝባችን ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ለማድረግ የበቃ ነው።

በወያኔ የአገዛዝ ዘመን የውጭ የስለላ ድርጅቶችና መንግስት ነክ የሆኑ የዕድገት አራማጅ ድርጅቶች ነን የሚሉት ከራሳቸው አንደበት የወጣውን ወንጀላዊ አሰራር ስሰማ አገራችን የቱን ያህል የተጋለጠችና በቀላሉ ልትወረርና ልትከፋፈል እንደምችል ለመረዳት ችያለሁ። ሁለቱንም ሰዎች በተለያየ ስብሰባ ላይ በአጋጣሚ የተገናኘን ሲሆን የነገሩኝ በሙሉ የሚያሳዝን ነው። አንደኛው አሜሪካን አገር የሚኖር  አሜሪካዊ ይሁዲ ሲሆን ከአነጋገሩ እንደተረዳሁት ስራው የስለላ ስራ ነው። ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመላለስ ከነገረኝ በኋላ ኢትዮጵያ የተሰረረች አገር ነች ብሎ እቅጩን ነገረኝ። በቀላሉ እንደምንታለልንና በተለይም የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንዲሁም የሚሊተሪ ኤሊቱ በቀላሉ እንደሚታለልና አገርን ለመሸጥ እንደተዘጋጁ አድርጎ ነው የነገረኝ። በጊዜው የአሜሪካን፣ የእስራኤል፣ የሳውዲ አረቢያና እንዲሁም የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የስለላ ሰዎች በመመላለስ ዛሬ ለወደቅንበት ትርምስ፣ የጎሳና የሃይማኖት ግጭት፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያናት መቃጠልና ምዕመናን መገደል ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ከሰውየው አነጋገርም ሆነ ነገሩን በጥብቅ ከሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን አፍ ለመስማት ችያለሁ። ሌላው ደግሞ በአንድ በዕድገት ስም በተካሄደ ሰሚናር ላይ የተዋወቅሁት ጀርመናዊ ያጫወተኝ ነው። ሰውየው አሁን ጡረታ ወጥቶ በርሊን ከተማ ይኖራል። ከኢትዮጵያ መምጣቴን ስላወቀ ብዙ ከተጨዋወትን በኋላ ኢትዮጵያና ሌሎች አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ጂቲዜድ አሁን ደግሞ ጊዝ(GIZ) ተብሎ በሚጠራው በጀርመን መንግስት በሚደገፍ የተራድዖ ድርጅት ውስጥ ሲሰራ እንደቆየ ይነግረኛል። የእኔም ጥያቄ ለመሆኑ ስራችሁ ምንድነው? ብዬ ስጠይቀው በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ድርጅቱ ምን ምን ነገሮች እንደሚሰራ ዘርዝሮ ነገረኝ። እንዳለውም ድርጅቱ በኢትዮጵያ ላይ ወንጀል እንደፈጸመና በዕርዳታ ስም ብዙ ነገሮችን ለማበላሸት ችሏል። ለምን እንደዚህ ታደርጋላችሁ? ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የአገራችሁ መንግስት ስላሳሳተን ወይም ስላታለለን ነው የሚል ነበር። እኔም ይህ ሊሆን እንደማይችል በዝርዝር አስረዳሁት። በመጀመሪያ የተወለድከው፣ ያደግከውና የተማርከው እዚህ ጀርመን አገር ነው። የተወለድክበትም አገር የተዝረከረከ አገር ሳይሆን በጥንቃቄና በስንትና ስንት ዕውቀት የተገነባ ነው። አንድ ሰው ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ወይም ሌላ የሶስተኛው ዓለም አገር ሲሄድ ወዲያውኑ የከተማዎችን አገነባብና አጠቃላይ ሁኔታውን ሲመለከት የአስተሳሰብ ብልሹነት እንዳለ ሊገነዘብ ይችላል። በመሆኑም አንድ የሶስተኛው ዓለም አገር አገዛዝ ከጀርመን የሄደን ምሁር ወይንም ኤክስፐርትን ሊያሳስተው በፍጹም አይችልም። ሁኔታው እራሱ የሚገልጽና መንግስት የሚባለውም ፍጡር የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳለውና ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ ፖሊሲ አገሩን እንደሚያተራምስ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ካልኩት በኋላ፣ እናንተ የምታደርጉት ሁሉ ሆን ብላችሁ ነው። የአንድ አገር የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ከተበላሸ በኋላ ይህንን ለማረም በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይም በኮንዶሚኒዩም ዙሪያ የተሰራውን ወንጀል አንተ ብቻ ሳትሆን ሌላ ከድርጅታችሁ ጋር የሚሰራ አርክቴክቸርም ነግሮኛል። እኔም ትክክል እንዳልሆነና አንድ መንደር በዚህ መልክ እንደማይሰራ ላስረዳው ሞክሬያለሁ። ይህ ነው እንግዲህ የወያኔ አገዛዝና በጠቅላላው ባለፉት 28 ዓመታት የተፈጠረው አዲሲ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት የሰሩት ወንጀል።

የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ስልጣን ሲረከብና ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ሲያወራ እሳቸው አባል የሆኑበት የወያኔ አገዛዝ ጥሎ ያለፈውን ተጨባጭና የህሊና ሁኔታ በሰፊው መገምገምና ለሰፊው ህዝብ በጽሁፍ ማቅረብ ነበረበት። እንደሚታወቀው አንድ በሽተኛ የህመሙ ዐይነት ሊታወቅ የሚችለው በሰፊውና በጥልቀት ከተመረመረና እራሱም በሽተኛው ተባባሪ ከሆነ ብቻ ነው። የዚያን ጊዜ ሀኪሙ ለህመምተኛው በሽታውን ሊፈውስለት ወይም ሊያድነው የሚችል ተቀራራቢ መድሃኒት ሊያገኝለት ይችላል። ማንኛውም ሃኪም በበቂው ሳይመረምር ዝም ብሎ መድሃኒት አያዝም። የአንድ ህብረተሰብ ጉዳይም በጥልቀትና በሰፊው ሳይመረመርና በሽታው ሳይታወቅ ስለለውጥ መናገር አይቻልም። በሌላው ወገን ደግሞ ለውጥ በሄደት የሚመጣ እንደመሆኑ መጠን መነሻውንና መድረሻውን ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህ ስንነሳ የዶ/ር አቢይና አገዛዛቸው ፖሊቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የድሮውን ዐይነት በሌላ መልክ የሚያራምድ እንጂ አገራችንን በሁለት እግሯ እንድትቆምና ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የሚያደርግ አይደለም። ከሁኔታውም መረዳት እንደሚቻለው ምንም ዐይነት ለውጥ እንደማይካሄድ ነው። በለውጥ ስም የሚካሄደው ነገር በሙሉ የውጭ ኢንቬስተሮች የሚባሉትን ለመሳብ የሚደረግ በደንብ ያልተጠናና የማይታወቅ የገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትን የተወሰነውን በክፍያ ስም መሸጥ በመሰረቱ የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም። ለሁለ-ገብ የአገር ግንባታና ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያመች አካሄድ አይደለም። የአገር ውስጥ ገበያ እንዳያድግና ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዳይዳብሩ የሚያደርግ የተበላሸ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ባጭሩ ለውጡ ከኒዎ-ሊበራሊዝም ወደ ባስ ኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንጂ፣  ህዝባዊ ባህርይ ወዳለው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ  የሚያስኬድ ለውጥ አይደለም። በሌላ ወገን ግን የለውጥ ኃይሎች የሚባሉት ስለለውጥ ሲያወሩ ለውጥ ማለት ምን ማለትና፣ በምንስ ፍልስፍና ወይንም ራዕይ ላይ መመስረት እንዳለበት የገባቸው አይመስልም። አንድ አገዛዝ የሚመራበትን ራዕይ በደንብ የማያውቅ ከሆነ አስተዳድረዋለሁ ወይም እገዛዋለሁ የሚለውን ህዝብ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ነው የሚያደርገው። ፈጣሪና ታታሪ፣ እንዲሁም በእሴትና በሞራል የታነፀ ትውልድ የሚያፈራ ሳይሆን ባለፉት 28 ዐመታት እንደታየው እሴተ-አልባና አገር ወዳድ ያልሆነ ትውልድ ነው የሚያፈራው።  

በአጠቃላይ ሲታይ ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የፖለቲካ አጀንዳው ከዲሞክራሲና ከአጠቃላይ ነጻነት በማግፈግፈግ ወይም በመወርወር  በብሄረሰብ ላይ ወደ ተመሰረተ አምባገነናዊ፣ እንደ ኦሮሚያ ባሉት ክልሎች ደግሞ ወደ ፋሺሽታዊ አገዛዝና ጽንፈኝነት ወደ ሰፈነበት ስርዓት እየተጓዘ ነው ማለት ይቻላል። ከግለሰብአዊ ነፃነትና በሪፑብሊካናዊ አሰተሳሰብ ላይ ከተመሰረተ የህግ የበላይነት ይልቅ የጎሳ ፋሺዝም ቦታውን በመውሰድ በየቦታው አለመረጋጋት ተፈጥሯል። የየክልል አስተዳዳሪዎች የጠራና ለሁሉም ኗሪው ህዝብ የሚሆን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመንደፍና ሁሉንም ያካተተ አስተዳዳራዊ መዋቅር ከመዘርጋት ይልቅ፣ መጤ ጎሳ እያሉ እያዋከቡና የማግለል ፖለቲካ እያካሄዱ ነው። አንዳንድ የክልል መሪዎች በፍልስፍና የሰለጠኑና የፕላቶንን የሪፑብሊክ መጽሀፍ ያነበቡ  ናቸው ቢባልም የሚያካሂዱት ፖለቲካ የፕላቶንን ትምህርት እንዳለ የሚቃረን ነው። በመንፍስ የበላይነት የሚመሩ ሳይሆን ጊዜው የእኛ ነው፤ ይህ ጊዜ ካመለጠን እንደገና ተመልሰን የበላይነታችንን አንቀዳጅም በማለት የጭቆናና የማስፈራራት አገዛዛቸውን እያጠናከሩ ነው።  ባጭሩ ከህዝባዊ ሶሊዳሪት ይልቅ የጎሳ ሶሊዳሪቲ እንዲጠናከር በማድረግ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሁኔታውን እያመቻቹ ነው። ከዚህ በተረፈ በአገር አቀፍ ደረጃ የመንግስቱ መኪና በኦነግና በሌሎች የኦሮሞ ጽንፈኛ ኃይሎች በመሰግሰግ አገዛዙ ወደ ጨቋኝነት አምርቷል። ፍርድ ቤቶችና አቃቤ ህጎች አደገኛ ጨዋታ እየተጫወቱና የግለሰብም መብት በከፍተኛ ደረጃ እየተገፈፈ ነው። ባጭሩ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ የፖለቲካ ሜዳውን በሳውዲ አረቢያና በግብጽ፣ እንዲሁም በሲአይኤ ለሚደገፉና በገንዘብ ለሚደጎሙ እንደነጃዋር ለመሳሰሉ ኃይሎች ክፍት በማድረግ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደሚጣ በማድረግ ላይ ነው። ባለፈው አንድ ዐመት ቁጥራቸው በግልጽ የማይታወቁ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል። አንዳንዶችም ካለምንም ማስረጃ በአሸባሪነት ስም በመወንጀል ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። ሌሎች ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ተጥለዋል። ቤተክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ምዕመናንም ተገድለዋል። ከዚህ በስተጀርባ እነ ሳውዲ አረቢያና ቱርክ እንዲሁም ግብጽ የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዳሉበት ግልጽ ነው። እነዚህ ኃይሎች በማህበራዊ ወይም በሶሻል ስም እያሳበቡና እየተመላለሱ፣ ወይሞ ካለምንም ዕቅድና ፍላጎት መስጊዶች እንዲሰሩ በማድረግ አደገኛ ጨዋታ እየተጫወቱ ነው።  የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹም የኢትዮጵያን መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዕድገቷን በፍጹም አይፈልጉም። የምትሽመደመድ ኢትዮጵያንና፣ ቡናና ስኳር፣ እንዲሁም አበባን እያመረተች የምታቀርብ ኢትዮጵያን ነው የሚፈልጉት። ዋና ዓላማቸውም በአፍሪካ ምድር እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ እንዲሁም ቻይና የመሳሰሉ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የበለጸጉና ያደገ የውስጥ ገበያ ያላቸው አገሮች ብቅ እንዳይሉ የተቻላቸውን ነገር  መስራት ነው። አተራማሽና ጦርነት ጫሪ ኃይሎችን በገንዘብና በፖለቲካ በመደገፍ የድህነት ዘመኑን ማራዘም ነው ዋና ስራቸው። ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የበላይነታቸውን ይዘው ሊቆዩ የሚችሉት ሌሎች አገሮች ሲዳከሙ ብቻ ነው። ኢምፔሪያሊዝምና ግሎባል ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስተካከለ ዕድገት እንዲኖር አይፈልጉም። ባልተስተካከለ ዕድገትና በተዛባ የንግድ ሚዛን አማካይነት ነው ሀብት እንደኛ ካሉት ኋላ-ቀር ከሚባሉ አገሮች ወደ ካፒታሊስት አገሮች የሚፈሰውና ካፒታሊዝም ሊደልብ የሚችለው። ከዚህ ውስጥ ዕዳ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት፣ በዕዳ የተተበተቡ አገሮች በዕዳ ወድመጥ ውስጥ በመግባት እዚያው በዚያው እንዲንደፋደፉ በማድረግ ድህነትን የማይቀርፍና የአገር ውስጥ ገበያን የማያሳድግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ። በዚህ መልክ አንድ አገር ሙሉ በሙሉ ብሄራዊ  ነፃነቷን በማጣት በዘለዓለማዊ ትርምስና አልፎ አልፎ በሚከሰት የእርስ በእርስ ጦርነት ሀብትና የሰው ጉልበት ይወድማል።  ባጭሩ እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ አገሮች በዘለዓለማዊ  ድህነት የሚማቅቁት በአንድ በኩል አገዛዞች ካለብዙ ምርምርና ጥናት፣ እንዲሁም ከአገራቸው የምጣኔ ሀብትና ከሰው ተጨባጭ ፍላጎት ውጭ ተግባራዊ በሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አማካይነት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን ዐይነቱን ከውጭ የሚመጣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመመርመርና በማጥናት ኢ-ሳይንሳዊ መሆኑን ለማሳየት የሚችል ምሁራዊ ኃይልና የሲቪክ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ነው።  ለማንኛውም አገራችን ዛሬ በውጭ ኃይሎች መንጋጋ ውስጥ በመግባት የምትታኘክ አገር ነች። ለአደጋ የተጋለጥችና አለኝታ ያጣች ነች። አገዛዙ ይህንን የተደቀነብንን አደገኛ ሁኔታ ለመከላከል ስትራቴጂ ከማውጣት ይልቅ ሆን ብሎ የያዘው በአገር ወዳዶች ላይ ዘመቻ ማካሄድ ነው። ጋዜጠኞችንና ኮሜዲያኖችን ማን ነው?  የሚከፍላችሁ ወይም ፋይናንስ የሚያደርጋችሁ በማለት ውስጣዊ ጥንካሬ እንዳይኖር በማድረግ ላይ ነው።

ወደ ሌሎች ጉዳዮች ስንመጣም እንደዚሁ የተምታታ ፖለቲካ እናያለን። 28 ዐመት በሙሉ ህዝባችንን ሲያስረብሹና ሀብት ሲዘርፉ የከረሙት እንደ ጌታቸው ረዳና ልደቱ አያሌው የመሳሰሉት፣ ሁሉም ነገር የተምታታበትና ወዳጁን ከጠላቱ የማይለየው በቀለ ገርባ የመሳሰሉ በሲአይኤ በሚደገፍ በሮታሪ ክለብና በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ተጋብዘው ዝቃጭ የሆነ ገለጻ ሲሰጡ ስናይ ፖለቲካው የቱን ያህል ግራ የገባው እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። ቀደም ብሎ እንደዚሁ የኢትዮጵያን የውጭ ፖለቲካ አስመልክቶ ገለጻ እንዲሰጡ የተጋበዙትና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሲሰሩና፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ሳይሆን የውጭ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቁትን ኤክስፐርት ነን ባዮች የሚናገሩትን ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍና አልባ  ሀተታ ስንሰማ የአገራችን ፖለቲካ የቱን ያህል እንደተበላሸና አወናባጅ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን።

የዶ/ር አቢይ ፖለቲካ በውስጡ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የገባውና ግልጽ ያልሆነው፣ የውጭ ፖለቲካውም አደገኛና የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነቷን የሚያስደፍር ነው።  የውጭ ፖለቲካው ከውጭ የሚመጣውን ጣልቃ ገብነትና አገር አፍራሽነትን ለመጋፋት ወይም ደግሞ ሊቋቋም የሚችል አይደለም። ግራ የሚያጋባ ሁኔታ በሚለው ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአሜሪካ ሞግዚትነት ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ተብሎ ፓርሊያሜንቱና ህዝብ ሳያውቀው አገዛዙ ከአሜሪካን ጋር ያደረገው ስምምነትና መፈራረም የተገፈፈውን ብሄራዊ ነፃነታችንን የባሰ የሚገፍና ነፃና ዲሞክራሲያዊ አገር፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ ጠንካራ የሆነች  አገር እንዳንገነባ የማያደርገን ነው። በቅርቡ ከውጭ የመጡ ወደ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች አገራችን ውስጥ መለማመድና የመከላከያ ሚኒሰተሩና አንዳንድ መኮንኖች አሜሪካን ሄደው ስልጠና ማግኘት፣ ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው የቱን ያህል የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ስር እንደወደቀ ነው። ይህ ዐይነቱ የእከክልኝ ልከክልህ ግኑኝነት የግዴታ የመንግስቱን መኪና የባሰ ጨቋኝና ነፃነትን አፋኝ ያደርገዋል። እነ ዶ/ር አቢይ ኢምፔሪያሊዝምና ግሎባል ካፒታሊዝም የሚሉት ጽንሰ-ሃሳቦች  የገባቸው አይመስልም። አሜሪካንና ግብረአበሮቿ፣ እንዲሁም ሳውዲ አረቢያና ሌሎች የተቀሩት የአረብ አገሮችና እስራኤል፣ ኢራክን፣ ሊቢያንና ሶርያን እንዴት እንዳፈራረሱና፣ በደቡብ የመን ደግሞ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ አድርገው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትና ሌላ ምስኪን ዜጎች እንዲያልቁ እንዳደረጉ በጥብቅ ተከታትለው ወይንም በውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩና በሌላ የአካባቢን ፀጥታ በሚከታተለው መስሪያ ቤት በኩል ማስረጃ ሰብሰበው እንደሆን ማወቅ በፍጹም አይቻልም። ለማንኛው በአገዛዙም ሆነ ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ኃይል ዘንድ የውጭ ኃይሎችን ሴራና አገርን አፍራሽ ፖለቲካ በሚመለከት ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ግልጽ ነው። በቅርቡ ልደቱ አያሌው በአንድ ውይይት ላይ በግልጽ እንደተናገረውና እንደሚያምንበትም የአገራችን ፖለቲካ ከአሜሪካን ቁጥጥር ውጭ እንደማይወጣ ነው።  ክአርባ ዓመት በፊት የተማሪው እንቅስቃሴና በጠቅላላው ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል የአሜሪካንን ጣልቃ ገብነትና የፀረ-ዕድገት ፖሊሲ አጥብቆ የተዋጋው የዛሬ ዐይነት ሁኔታ እንዳይከሰት ነበር። ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለው ከአርባ ዓመት በኋላ እንደገና የአሜሪካን የጭቆናና የፀረ-ዕድገት ስርዓት ውስጥ ወድቀን ስንመለከት አገራችን የቱን ያህል ሰው እንደሌለባት ነው የሚያረጋግጠው። የቱን ያህል የአፄ ቴዎድሮስና የአፄ ምኒልክ እንዲሁም የብዙ ጀግኖቻችን ህልም ባክኖ እንደቀረ ወይም ተግባራዊ ለመሆን እንዳልቻለ ነው የምንረዳው። ከዚህ ስንነሳ አገራችን ከአሜሪካን መንጋጋ ካልተላቀቀች በምንም ዐይነት ነፃና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊፈጠር አይችልም። ህዝባችንም ጠንካራና የሚያስተሳስረው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹ አይችልም።

መደምደሚያ!

አጠቃላዩን የአገራችንን ሁኔታና በፖለቲካው ውስጥ በመሳተፍ ወዲህና ወዲያ የሚራወጡትን ኃይሎች ሁኔታ ስንመለከት ፖለቲካ የሚለው ትልቅ ፅንሰ-ሃሳብ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ነው የምረዳው። በግለሰብም ሆነ በድርጅት ዙሪያ ተሰባሰብን የሚሉ ሰዎች ስለ ፖለቲካ እየደጋገሙ ቢያወሩም ራዕያቸው ወይም የፖለቲካ ፍልስፍናቸው በግልጽ አይታወቅም። ሁላችንንም ያሰባሰበው ኢትዮጵያ የሚለው ስምና ባንዲራችን ቢሆኑም በአብዛኛዎቹ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ዘንድ በኢትዮጵያ ምድር 110 ሚሊዮን ህዝብ እንደሚኖርና፣ ይህም ህዝብ ህልምና ፍላጎት እንዳለው በግልጽ የሚያውቁት ነገር የለም። ዝም ብሎ ብቻ በኢትዮጵያ ስም የሚናፈሰው ፖለቲካ ወደ አጉል ብሄረተኝነት ወይም ናሺናሊዝም በመቀየር መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች እንድንርቅ እየተደረግን ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ አጉል አካሄድ የተለያየ ብሄረሰብን እንወክላለን በሚሉ ግራ በገባቸው ወይም ፍልስፍና-አልባ በሆኑ ኤሊቶችና የዘረኝነትን ፖለቲካ እንቃወማለን በሚሉት ዘንድ የሚካሄድ ቅጥ ያጣ ፍጥጫ ሆኗል። ትላንት አማራን ሲበዘብዝና ሲያስጨርስ የከረመው ዛሬ የአማራ ጠበቃ ሆኖ ይቀርባል። እንዲሁም የትግሬን ብሄረሰብ ሲያሰቃየውና ሲያደነቁረው የከረመው ህወሃት በህዝቡ ስም በመነገድ የእሱን ፋሺሽታዊ ፖሊሲ የተቃወመ ሁሉ ተቃውሞው በትግሬ ህዝብ ላያ ያነፃፀረ ነው በማለት ትግሉ በህዝቦች ዘንድ ይመስል ከፍተኛ የውንብድና ትግል እያካሄድ ነው። እንዲሁም ዛሬ ስልጣንን የተቆኖጠጡትና በዶ/ር አቢይ ዙሪያ የተሰባሰቡት የኦሮሞ ኤሊት አቀንቃኞች 27 ዐመት በሙሉ ሲያሰቃያቸው፣ ሲያስራቸውና ሲገድላቸው፣ እንዲሁም ከመሬታቸው ሲያፈናቅላቸው የከረመውን የህውሃትን አገዛዝ እርግፍ አድርገው በመርሳት የአማራውን ብሄረተኝነት ማዳከምና መደምሰስ አለብን በማለት የሞት የሽረት ትግል ያካሄዳሉ። አንዳንዶችም ፈቃድ የተሰጣቸው በሚያስመስል መልክ የኢትዮጵያ አንድነትና የስልጣኔ መሰረት በሆነው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ በመነሳት ቤተ-ክርስቲያናትን ያቃጥላሉ፤ ካህናትን ይገድላሉ። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ደግሞ ትላንትም ሆነ ዛሬ ከሲአይኤ ጋር ሲሰራ የከረመውና አብዮቱ እንዲከሽፍ ያደረገውና፣ ወያኔ ሰተት ብሎ እንዲገባ መንገዱን ያመቻቸለት እቺ አገር ልትበታተን ነው እያለ የውሸት ጩኸቱን ያሰማል። በጣም ግራ የሚያጋባ ሁኔታ!!

በዚህ ዐይነት በተመሰቃቀለና ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ ግልጽ የሆነ ትንተና የሚሰጥና በአንዳች ፍልስፍና ላይ በመመራት አገሪቱን ከተጋረጠችበት አደጋ ሊያድናት የሚችል አገር ወዳድ ድርጅት ብቅ ብሎ ሲታገል አይታይም። እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ስም የሚካሄደውን ትግል ስንመለከት ትግሉ የተራማጅነት ባህርይ የለውም። ጭንቅላትን ክፍት የሚያደርግና ጥያቄ በመጠየቅ መልስ እንድንሰጥ የሚያስችለን አይደለም። ትግሉ እጅግ ወደ ኋላ የቀረና ወደ ኋላ እንድንመለከት የሚያደርግ ነው። ፍልስፍናዊ፣ ሳይንሳዊና የቲዎሪ ባህርይ የለውም። ወዲህና ወዲያ የሚራወጡት ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች አክቲቪስት ባህርይ ያላቸውና በሴንሴሽናል ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ እንጂ ስትራቴጂክ በሆኑ ነገሮች ላይ የሚከራከሩና የሚያታግሉ አይደሉም። ትግላቸው የፕሮፌሽናል ባህርይ የሌለውና አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ዕውቀት በሌላቸው ሰዎች የሚታጀብ ነው። የሚታወቁትም ግለሰቦችና ድርጅቶች የፊዩዳል ባህርይ ያላቸው ስለሆነ እንደነዚህ ዐይነት ተከታዮችንና በጭፍን አሜን የሚሉትን ነው የሚመርጡት። ለግልጽ ውይይትና ክርክር ክፍት ያልሆኑ ኃይሎች የፖለቲካ መድረኩን በመያዝ ፖለቲካን ከህዝባዊና ከአገራዊ ባህርይ ነጥለው ለኢትዮጵያ እንታገላለን በማለት ሰፊውን ህዝብ፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱን ግራ እያጋቡት ነው።

ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት ዛሬ ታላቅና የተከበሩና እንዲሁም የሚፈሩ እንደ ቻይናና የቀድሞዋ ሶቭየት-ህብረት፣ አሁን ደግሞ ራሽያና እንደ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን የመሳሰሉ አገሮች እራሳቸውን ነፃ ያወጡትና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የበቁት ፍልስፍና ወይም ራዕይ-አልባ ትግል በማካሄድ አይደለም። ወይንም ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን በመለማመጥ አይደለም ወደ ውስጥ ያተኮረና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ አገር ለመገንባት የበቁት። ከእነዚህ አገሮችና ከካፒታሊስት አገሮችም ልምድና ተመክሮ የምንረዳው አንድ አገር ሊተሳሰርና ህዝቡም አገሩን አገሬ ነው ብሎ ሊጠራ የሚችለው አገሩ በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ሲገነባለት ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ህዝብ እራሱን እንዲያውቅና እንዲተሳሰር ከተፈለገ መንፈሱን ሊሰበስብ የሚያስችለው ዕውቀት ያስፈልገዋል። ሰፊው ህዝብ የመማር ዕድል ሲያገኝ ብቻ ነው ሁሉም ነገር ሊገለጽለትና ጥያቄም ሊጠይቅ የሚችለው። ያልተማረ ህዝብ  ደግሞ ዝም ብሎ የሚነዳና ከውጭ የሚመጣ አጉል ባህል ሰለባ የሚሆን ነው። ከዚህ ስንነሳ ትግሉ በአዲስ መልክ የሚካሄድና በአዲስ ፍልስፍና የሚመሰረት መሆን አለበት። ሊያሰባስበንና ጥንካሬ ሊሰጠን የሚችል መሆን አለበት። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                  fekadubekele@gmx.de