[gtranslate]

የአገራችን ኢኮኖሚ  የገበያ ኢኮኖሚ፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ፣ በመንግስት የሚደገፍ ኢኮኖሚ፣

ወይስ ሌላ !

                                                                       ፈቃዱ በቀለ፣ (ዶ/ር ) 

                                                           መጋቢት 13  2019 .

 መግቢያ

በቅድሚያ ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፣ በአለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት በአገራችን ምድር የነፃ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በተሳሳተ መልክ የሚናፈሰውንና በአንዳንድ መጽሄቶች የሚወጣውን የተሳሳተ አመለካከት ለመዳሰስ ነው። በተለይም ተማርን በሚሉትና በመንግስት በኩል የነፃ ገበያን በሚመለከት የተዛነፈና ከሳይንስና ከህብረተሰብ ግንባታ ጋር ሊሄድ የማይችል አባባል ሲናፈስ ይሰማል። ስለሆነም ይህንን የተዛነፈና ለአገር ግንባታ የማይበጅ አነጋገር የግዴታ በሳይንስ መነፅር መመርመሩ አስፈላጊ ይመስለኛል። በተጨማሪም ውጭ አገር የሚኖሩ በኢኮኖሚክስ ሙያ የሰለጠኑ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የገበያን ኢኮኖሚ ልቅ እንደሆነ ስርዓትና፣ ለሁሉም ተዋናይ የሀብት ክፍፍልን በእኩልነት ደረጃ እንደሚያዳርስ አድርገው ስለሚያቀርቡ የገበያ ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስልና በምንስ ዐይነት ውስጣዊ ህጎች እንደሚገዛ ማሳየቱን አመንኩበት። በሳይንስና በህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ባልተደገፈ ማስረጃ ስለገበያ ኢኮኖሚ የሚናፈሰው አባባል ድህነት እንዳይቀረፍና ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ የሚያግድ እጅግ አደገኛ አነጋገር ነው።  በሌላ ወገን ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ አባባልና በገበያ ኢኮኖሚ ስም ተግባራዊ  የሚሆነው ፖሊሲ ጥቂት ሰዎችን የሚጠቅምና የሚያደልብ ለመሆኑ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በተግባርም እንዳየነው በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖችና የምዕራብ መንግስታት የሚደገፈውና ተግባራዊ የሚሆነው   „የነፃ የገበያ“ ፖሊሲ አዳዲስ ችግሮችን በመፍጠርና፣ በድሮው ላይ በመደረብ ህዝቦችን የባሰውኑ ለድህነት መዳረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ተከታታይ ገዢዎችም እየተደራረበ የሚመጣውን ችግር ሊፈቱ የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ይታያል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው የሚተላለፍ የተወሳሰበ ችግር እየተፈጠረ በተለይም እንደኛ ያሉ የሶስተኛው ዓለም አገሮችን በማያቋርጥ ውዝግብ ውስጥ እንዲገኙ ለመደረግ በቅተዋል። የአንድ አገር ህልውናና ዘላቂነት የሚኖረው ማህበረሰብ መገንባትና፣ እንዲሁም ብሄራዊ ነፃነት መከበር ከትክክልኛ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን ስለ ገበያ ኢኮኖሚ የጠራ አመለካከት እንዲኖረን ይገባል።

ወደ አገራችን ስንመጣ ዛሬ በአገራችን ምድር የተስፋፋው ድህነትና የጥቂቶች ማበጥ ስለ ገበያ ኢኮኖሚ ያለን ግንዛቤና የፖሊሲው ውጤት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። በተለይም የህብረተሰብ ታሪክን ዕድገት በደንብ ሳይመረምሩና፣ እንደኛ ባሉ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆኑትን የኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ በተለይም ደግሞ ከምዕራቡ የካፒታሊስት ኢኮኖሚና፣ እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያና ከጃፓን ጋር ሳያነፃፅሩ የሚሰነዘር ሃሳብ የተከታታይ ትውልድን ህይወት እንደሚያበላሽና ታሪክን እንደሚያዛንፍ የታወቀ ጉዳይ ነው። ስለሆነም መጠየቅ ያለበት ጉዳይ የምዕራቡ ካፒታሊዝምና አንዳንድ የአሺያ አገሮች አነሰም በዛም በሳይንስና በቴኮኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የውስጥ ገበያና ህብረተሰብ ሲገነቡ ለምን እንደኛ ያሉ አገሮች ተሳናቸው ? አሁንስ ደሃና ለማኝ ለምን ሆኑ ብሎ መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም 27 ዓመት ያህል በዓለም ኮሙኒቲው የሚደገፍ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ቢሆንም ለምን ድህነት ሊቀረፍ አልቻለም? ለምንስ ጠንካራና የተሳሰረ የውስጥ ገበያ በአገራችን ምድር ሊዳብር አልቻለም ? ብሎ እየደጋገሙ ጥያቄ ማንሳት በጣም አስፈላጊ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ስለነፃ ገበያ በሚወራበት ጊዜ እንዲያው ዝም ብሎ ሳይታኘክና ሳይብላላ የሚወራ ነገርና ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ የመጨረሻ መጨረሻ አንድን አገር የመበታተን ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። ስለሆነም ስለነፃ ገበያ ፍቱነት በሚወራበት ጊዜ ትምህርትቤት ከተማርነው ባሻገር ሄደን ተጨባጭ ሁኔታዎችን መመርመሩ ስለነፃ ገበያ የተሻለ ስዕል ይሰጠናል። አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ገበታ ላይ የሚስጥ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ከዕውነት የራቀ ስለሆነ በመጽሀፍ የቀረበውን ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ማወዳደር ግዴታ ነው። ሳይንሳዊ ምርምርና ጥናት ከሚታዩ ነገሮች የሚፈልቁ እንደመሆናቸው መጠን ማንኛውም ምሁር ነኝ ባይ የአንድን አገር ተጨባጭ ሁኔታ የግዴታ መመርመር አለበት።  ስለሆነም አስተማሪዎች በተሳሳተ መልክ ትምህርትቤት የሚሰጡትን ትምህርት እንደ እግዚአብሄር ቃል አድርጎ መውሰድ ከሳይንስ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ትምህርትቤት ገብተን የምንማረውንና የሚነገረንን እሱን እንደ ዕምነት ለመቀበልና መልሰን ለማስተጋባት ሳይሆን፣ ከኮመን-ሴንስም ሆነ ከሳይንስ አንፃር ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን በመመርመር የራሳችንን ፍርድ ለመስጠትና ትክክለኛውን መንገድ ለመያዝና ለሌላው ደግሞ ለማሳየት ነው። የተማሩ ሰዎችም ዋናው ተግባርና ኃላፊነት አንድን ነገር ከሳይንስና ከተጨባጩ ሁኔታ በመመርመርና በማጥናት ለሰፊው ህዝብ ዕውነትን ከውሸት ለመለየት ይችል ዘንድ ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ነው።

በተለይም ባለፉት ስድሳ ዐመታት የኒዎ-ክላሲካል፣ ወይም በዘመኑ አባባል ደግሞ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የበላይነትን ከተቀዳጀ ወዲህ፣ በብዙ መቶሺህ የሚቆጠሩ ምሁራንን በማሳሳት ለብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ድህነትና ኋላ-መቅረት ዋናው ምክንያት እንደሆነ በየአገሩ የሰፈኑት ተጨባጭ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ እሱን የሚቀናቀኑ አያሌ የኢምፔሪካልና የቲዎሪ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በተለያዩ አዋቂዎች ታትመው የወጡትን የተለያዩ አስተሳሰቦችን ያዘሉና፣ በየአገሩ የሰፈኑትን በጣም አስከፊ ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ማወዳደርና እንዲሁም ደግሞ ማውጣትና ማውረድ ባልተለመደበት እንደኛ ባለ አገር ከአንድ ወገን የሚቀርቡ ትምህርቶችን ትክክል ናቸው ብሎ መቀበልና እነሱን ማስተጋባቱ እንደልማድና ዕምነት ተደርጎ ተወስዷል። ይህን የመሰለ የተሳሳተ አባባል በተፈጥሮ ሳይንስም ውስጥ ተቀባይነትን በማግኘት የሳይንስን ዕድገት ሁለት ሺህ ያህል ዐመታት አፍኖ እንዳስቀረ ይታወቃል። ለምሳሌ የፕላኔቶችን፣ ምድርንም ጨምሮ በፀሀይ ዙሪያ መሽከርከር በብዙ የግሪክ ፈላስፎች የታወቀ ቢሆንም፣ አርስቲቶለስና ፖትሌመዎስ ይህን ሀቅ በመገልበጥ፣ ፀሀይ ሳትሆን በአንድ ቦታ ቆማ የምትገኘው ምድር ናት በማለትና፣ ፀሀይና ሌሎች ፕላኔቶችም በምድር ዙሪያ ነው የሚሽከረከሩት ብለው የሳይንስን ዕድገት እንደጎተቱትና፣ የአውሮፓም ህዝብ ለሰባት መቶ ዐመታት ያህል በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል። በተለይም በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች ተቀባይነትን ያገኘው ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ዕምነት በኮፐርኒከስ ውድቅ እንዲሆን ከተደረገ ወዲህ፣ ጳጳሶች በሳይንቲስቶች ላይ በመነሳት አንዳንዶቹን እንዳቃጠሏቸውና፣ ጋሊልዮን ደግሞ እስር ቤት እንደወረወሩት ይታወቃል። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ዕውቀትን በሚመለከት የተለያዩ አመለካከቶች እንደመኖራቸው ሁሉ፣ በአንድ የታሪክ ወቅት የበላይነትን የተቀዳጀው ኃይል የሰው ልጅ ዕውነተኛውን የነፃነት መንገድ እንዳይከተልና፣ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነበት ኑሮ እንዳይመሰርት በተወሰኑ ምሁራን እንደ ዕውቀት የዳበሩትን ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ የሰውን ልጅ አስተሳሰብ እንዲጠብ ለማድረግ በቅተዋል። ወደ ውስጥ ጠልቆ እንዳይመራመር በማድረግ ለህብረተሰብአዊ ውዝግብ ዋና ምክንያት ለመሆን ችለዋል። በዚያው መጠንም ዕውነተኛ ስልጣኔን የመቀዳጀቱ ጉዳይ እየተራዘመና እየጨለመ እንዲሄድ ለመደረግ በቅቷል።

ወደ ኢኮኖሚክስ ስንመጣ ዛሬ በየትምህርትቤቱ የሚሰጠውና እንደቀኖና የተወሰደው የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ትምህርት ብቅ ከማለቱ በፊት ብዙ የአውሮፓ መንግስታት፣ ኋላም አሜሪካ ህብረ-ብሄርን(Nation-State) መገንባት የቻሉት የኔዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራልን የኢኖሚክስ ቲዎሪን መሰረት በማድረግ ሳይሆን –በጊዜው እንደዚሁ ዐይነቱ ቲዎሪ በፍጹም አይታወቅም ነበር- መንግስታት በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና በመታገዝና ጣልቃ በመግባት፣ እንዲሁም የነቁ ኃይሎችን በመደጎምና ውጤታማ የሆነ ኢኮኖሚያዊና የህብረተሰብ ግንባታ ፖሊስን ተግባራዊ በማድረግ ነው። ይህም የኢኮኖሚ ፖሊሲ መርከንታሊዝም በመባል ይታወቃል። የኋላ ኋላ ሌሎች የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች ቢፈልቁም፣ ከአስራአምስተኛው እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ማገባደጃ ድረስ የብዙ አውሮፓ መንግስታት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማኑፋክቱር ግንባታ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ የውስጥ ገበያን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት፣ ከተማዎችን ማስፋፋት፣ የካናል ሲይስተሞችንና የባቡር ሃዲድን በመስራትና በመገንባት ህዝቡን ማስተሳሰር ነበር። በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የአዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ መመሪያ ተቀባይነት እንዲኖረው በተለይ እንግሊዝ ከፍተኛ ትግል ብታካሂድም፣ የጀርመን ፈላስፎች፣ የህብረተሰብ ሳይንስ ምሁሮችና ኢኮኖሚስቶች ይህንን ዐይነቱን ልቅ የሆነና ለእንግሊዝ ብቻ የሚያመቸውን የነፃ ገበያ ፖሊሲ በመቃወምና የራሳቸውን ቲዎሪ በማፍለቅና በማስፋፋት ጀርመን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንድትገነባ መሰረት መጣል ችለዋል። በዚህም ማህበራዊና አገራዊ፣ እንዲሁም በማኑፋክቱር ላይ በተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ጀርመን እንግሊዝን በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ቀድማ ልትሄድ ችላለች።

የዩሊታሪያን አስተሳሰብ ከተስፋፋ በኋላ የነፃ ገበያ ፍልስፍና እንዳለ ለሰላሳ ዐመት ያህል እንግሊዝ አገር ተግባራዊ ቢደረግም ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ቀውስ በመፈጠሩና ድህነትም ስለተስፋፋ በጊዜው የድህነት ፖሊሲን መዋጊያ (Poor Law) በማውጣት፣ ሊሰራ የሚችል ሰው ሁሉ ስራን ሳያማርጥ በዝቅተኛ ደሞዝ እንዲሰራ ተገደደ። ልቅ የሆነ የነፃ ገበያ ፖሊሲ ውድቅ ከተደረገ በኋላም እንግሊዝም ሆነች ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በመንግስት የተደገፈን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ ተገደዋል። በሌላ ወገን ግን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይና በጀርመን መሀከል የነፃ ንግድ ስምምነት ቢደረግም፣ ይህ ዐይነቱ የነፃ ንግድ ስምምነት በጀርመንና በፈረንሳይ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ስላደረሰ ሁለቱም አገሮች ስምምነቱን በማፍረስ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ ተገደዋል። የኢኮኖሚክስ ታሪክን ሊትሬቸሮችና፣ በተለይም በኋላ በማርክስ የተደረሰውን የዳስ ካፒታልን ስራና፣ የሹምፔተርን የኢኮኖሚ ዕድገት መጽሀፍና፣ እንዲሁም ሌሎች ትችታዊ አመለካከት ያላቸውን መጽሀፎች ላገላበጠ የሚረዳው በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተካሄደው የኢኮኖሚ ግንባታ በፍጹም አዳም ስሚዝም ሆነ በኋላ የወጣው የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚነግሩን አይደለም። ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊታይ የቻለው በስምምነት ላይ ወይም ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ጥቅም በማስቀደምና ኢኮኖሚያዊ „ግለሰብአዊ አርቆ-አሳቢነትን“ መመሪያ በማድረግ አይደለም። የካፒታሊዝም ዕድገት፣ ወይም ደግሞ በማሳመር የነፃ ገበያ ተብሎ ስም የተሰጠው ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ብዙ ውጣ ውረድን አሳልፎ እዚህ የደረሰና፣ በተወሰኑ አገሮች ውስጥ ብቻ ተግባራዊ የሆነ ክንውን እንደሆነ የኢኮኖሚክስ ታሪክ መጽሀፎችና የህብረተሰብ ታሪክ ግንባታ ሊትሬቸሮች ያረጋግጣሉ። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት በተካሄደባት እንግሊዝ አገር ውስጥ የካፒታሊዝም አፀናነስና አስተዳደግ ከውስጥ ገበሬውን በማፈናቀልና ወደ ከተማ እንዲሰደድ በማድረግ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል። ካፒታሊዝም ወደ ገጠር ሲስፋፋ በእርሻ ላይ የተሰማራው የፊዩዳል መደብ በዕድገት ላይ የሚገኘውን የሱፍ(የልብስ) ኢንዱስትሪ የጥሬ-ሀብት ፍላጎት ለማሟላት ሲል በበግ እርባታ ላይ ተሰማራ። ይህ ሁኔታ የትናንሽ ገበሬዎችን አስተራረስ እንዲቀይር ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛው ገበሬ ከሚያርስበት እንዲፈናቀል በመደረጉ፣ በተለይም እንደለንደን ወደ መሳሰሉት ከተማዎች እንዲሰደድ ተገደደ። በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ያገኘው ሰራተኛ ደግሞ የስራው ሁኔታ እጅግ አሰቃቂና አሰልቺ፣ እንዲሁም ደግሞ በጣም አድካሚ እንደነበር በኢኮኖሚክስ የታሪክ ምሁራን በደንብ ተተንትኖ ተቀምጧል። ይህ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ያላገኘው ሰፊ የሰራተኛው መደብ(reserve army) የግዴታ በመንገድ ስራ፣ በካናልና በድልድይ እንዲሁም ትላልቅ ቤተመንግስቶችንና ካቴድራሎችን ለመስራት ይገደድ ነበር። ዛሬ በብዙ ምዕራብ አውሮፓ ዋና ዋና ከተማዎች የምናያቸው የሚያማምሩ ትላልቅ ህንፃዎች በሰፊው ህዝብ ደም የተገነቡ ናቸው። የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚለን እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ሲል በኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ በመሳተፍ የገነባው አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር በኒዎ-ክላሲካል የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ ውስጥ ከተማዎችና ህንፃዎች ምን እንደሆኑ አይታወቁም። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ክንውን ካለቦታና ካለጊዜ የሚካሄድ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ደግሞ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ታሪክ ነው። ይሁንና በሬናሳንስ አማካይነት የተካሄደው ጭንቅላትን የማደስ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ለግለሰብአዊ ፈጣሪነት መንገዱን እንዳመቻቸ የማይታበል ሀቅ ነው። የገበያ ኢኮኖሚ እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ ከመወሰዱ በፊት ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ በተለይም በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የተካሄደው ቅድመ-ስራ የአሪስቶክራሲውንም ሆነ በማደግ ላይ የነበረውን የከበርቴ መደብ፣ እንዲሁም ደግሞ ሰፊውን ህዝብ ጭንቅላቱን በአዲስ ዕውቀት አድሶታል። ኋላ-ቀር ከሆነ የፊዩዳልና ሌሎች ስልጣኔን ከሚቀናቀኑ አስተሳሰቦች እንዲላቀቅ ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ ይሰራ ነበር። ስለሆነም ስለካፒታሊዝም ወይም ደግሞ በብዙዎች አነጋገር ስለገበያ ኢኮኖሚ ሲወራ ከላይ ባጭሩ የሰፈረውን ሀተታ ከቁጥር ውስጥ ሳያስገቡ ዝም ብሎ የነፃ ገበያ እያሉ መወትወት እንዲያውም የባሰውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ እንደመታገል ነው የሚያስቆጥረው። ይህም ማለት፣ ስለ ገበያ ኢኮኖሚ ከመወራቱ በፊትና፣ ካለሱ ፍቱን መፍትሄ የለም እያሉ ከመወትወት በፊት በመጀመሪያ ለካፒታሊዝም መፀነስ ቅድመ-ሁኔታዎች ከሆኑ ነገሮች ጋር መተዋወቅ ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ካፒታሊዝም ደረጃ በደረጃ ያለፈባቸውን የታሪክ ሂደቶች መመርመርና፣ ዛሬ ደግሞ እንዴት አድርጎ የብዙ ቢሊዮንን ህዝቦች ዕድል መወሰን እንደቻለ በሰፊው ማጥናት ያስፈልጋል። በህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የተደረገውን ትግልና ጥረት፣ እንዲሁም ደግሞ የተለያየ አስተሳሰብ በነበራቸው ምሁራን ዘንድ የተደረገውን የጦፈ ክርክር ሳያጠኑ ተግባራዊ የሚሆኑ የኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነትን ያስከትላሉ። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ያደረጉ የላቲንና የአፍሪካ አገሮች ሁኔታ የሚያረጋግጠው፣ በውጭ የተደነገገና ምሁራዊ ክርክር ሳይደረግበት ተግባራዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድን አገር የቱን ያህል መቀመቅ ውስጥ እንደሚከተውና  በቀላሉ ሊወጣ የማይችል ዕዳ ውስጥ እንደሚከተው ነው።

ነፃ ገበያ ወይስ ካፒታሊዝም !

ነፃ ገበያ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ብቅ ከማለቱና ከመስፋፋቱ በፊት ብዙ አገሮች ከሞላ ጎደል የገበያን ኢኮኖሚ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ አዳብረዋል። ገበያ ከህብረተሰቦች ዕድገትና ከስራ-ክፍፍል መዳበር ጋር የተያያዘ ነው። ህዝቦች እንደማህበረሰብ ሲደራጁና ፍላጎታቸውም እያደገ ሲመጣ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ምርቶች ስለማያመርቱ፣ እያንዳንዱ ፍላጎቱን ለማሟላት ሲል አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል ማምረት የማይችለውን ለማግኘት ሲል ከሌላው ጋር መገበያየት ተገደደ። በገበያ ውስጥ በሚደረግ የተለያዩ አምራቾች ግኑኘነትና፣ በኋላ ደግሞ በነጋዴዎች አማካይነት እያንዳንዱ ግለሰብ፣ በመጀመሪያ ዕቃን በዕቃ(Natural Exchange)፣ በኋላ ደግሞ ገንዘብ የዕቃዎች ወይም እህል መለዋወጫ መሳሪያ ሆኖ ሲዳብር ተጠቃሚው የፈለገውንና የቻለውን በመግዛት ፍላጎቱን ያሟላ ነበር። እንደዚህ ዐይነቱ የገበያ ልውውጥ እንደ ህብረተሰብ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በተወሰነ ክልል በመካሄድና በማደግ፣ በኋላ ደግሞ በተለያዩ አገሮች መሀከልም በመስፋፋት የሩቅ ንግድ እየተባለ ለሚጠራው በር ከፈተ። በሩቅ ንግድ አማካይነትም በተለያዩ አገሮች ዘንድ የዕቃ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን፣ የባህልም ግኑኝነት በመፈጠር፣ በጋብቻና በመዋለድ ለአንዳንድ አገሮች የህብረተሰብአዊ ለውጥ እምርታን አምጥቷል። በተለይም  በእንደዚህ ዐይነቱ የሩቅ ንግድ ግኑኝነትና የዕቃዎች ልውውጥ ተጠቃሚና፣ ህብረተሰብአዊ ለውጥን ማምጣት የቻለው የምዕራብ አውሮፓ ነው። በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ነው በሩቅ ንግድ አማካይነት ቀስ በቀስ የስራ-ክፍፍል መዳበር የቻለውና፣ ነጋዴዎችም ብዙ ገንዘብ በማከማቸትና የዕደ-ጥበብ ስራዎችን በመቆጣጠርና የፊዩዳሉን መደብ በዕዳ በመተብተብና፣ ልዩ የፍጆታ አጠቃቀም በማስለመድ ቀስ በቀስ ወደ ኢንዱስትሪ ከበርቴነት ሊለወጡ የቻሉት። በአውሮፓ የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ  ከፊሉ የነጋዴ መደብ ወደ ኢንዱስትሪ ከበርቴነት ሲቀየር ዋና ተግባሩ ዝም ብሎ ሀብት ማጋፈፍ ብቻ ሳይሆን፣ በባህላዊ እንቅስቃሴና በከተማዎች ግንባታ ስራ በመሰማራት የህብረተሰቡ አኗኗር በዕውቅ(Rationalize) ላይ እንዲገነባና እንዲንቀሳቀስ ማድረግም ነበር። በዚህም ምክንያት በዕውቅ ላይ ያልተመሰረተው የፊዩዳሉ ስርዓት፣ በከተማዎች ግንባታ፣ በዕደ-ጥበብ ሙያ መስፋፋትና በንግድ ማበብ እየተዳከመና፣ ለሌላና ለተሻለ የአኗኗር ስርዓት መንገዱን እንዲለቅ ተገደደ። ፍልስፍና፣ ድራማና አርክቴክቸር ሲያብቡ፣ በተለይም የከበርቴውና የአርስቶክራሲው የአኗኗር ስልት ሲሻሻልና የአስተሳሰብ ለውጥም ሲጎለምስ አግዛዞች ህብረተሰቡ ሊተሳሰር የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያዘጋጁ ተገደዱ። በነሼክስፔር፣ በሼሊና የኋላ ኋለ ደግሞ በጀርመን ክላሲኮች የድራማና የክላሲካል ሙዚቃ አማካይነት በማደግ ላይ የነበረውን የከበርቴ መደብና የአርስቶክራሲ አገዛዝ ጭንቅላት እንዲታነጽ በማድረግ የከበርቴው ሰብአዊነት ቀስ በቀስ ሊስፋፋ ቻለ። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከህብረተሰብአዊ ዕድገት ጋር ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ሆኖ ተቀባይነትን በማግኘት ስራዎች በሙሉ ጥበብንና(aesthetic)  ስርዓትን እንዲይዙ ተደረጉ።

ከዚህ ባሻገር፣ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ በየጊዜው የህዝብ ቁጥር እያደገ ሲሄድና ፍላጎትም ሲጨምር ብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በአንድ ዐመት ውስጥ ሶስት ጊዜ ሊያመርቱ የሚችሉበትን ሁኔታ(The Three Field Farming System) አዳበሩ። በተጨማሪም በበሬ ከማረስ ይልቅ በፈረስ እየታገዙ በማምረት ምርት ሊያድግ የሚችልበት ሁኔታ ተዘጋጀ። በአገር ውስጥ ምርት ብቻ የህዝብ ፍላጎት ማሟላት ባልተቻለበት አገሮች ውስጥ መንግስታት ከውጭ እህል በማስመጣት የህዝቡን ፍላጎት ያሟሉ እንደነበር የተገደዱበት ጊዜ ነበር። ይህንን ጉዳይ ፕሮፌሰር ሚስኪሚን ሃርይ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ዘመን የሬናሳንስ ኢኮኖሚ(The Economy of Later Renaissance Europe, 1460-1600) በሚለው መጽሀፋቸው ውስጥ በዝርዝር ያስረዳሉ። በተጨማሪም ፕሮፌሰር ጞልድትዋይት፣ የሬናሳንስ ኤኮኖሚ በፍሎሬንሰ( The Economy of Renasissance Florence) በሚለው ግሩም መጽሀፋቸው የኢጣሊያን ኢኮኖሚ በዘፈቀደ ሳይሆን በዕውቅ ላይ የተገነባና፣ ጣሊያንም በተለይም በኢንዱስትሪ ምርት አይላ ትገኝ እንደነበር ነው የሚነግሩን። ከነዚህ መጽሀፎችም ሆነ ከሌሎች አያሌ የኢምፔሪካል ጥናቶች መረዳት የሚቻለው፣ በነፃ ገበያ አማካይነት ሁሉም እንደፈለገው እህሉን ውጭ እያወጣ መቸብቸብ ይችላል የሚባል አነጋገር የተለመደ ሳይሆን፣ በዕውቅና በመጀመሪያ ደረጃ የየህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት ያስፈልጋል የሚለውን መመሪያ በመውሰድ ነው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ህብረተሰብአዊ ግንባታ ሊካሄድ የተቻለው። ማንም እንደፈለገው መሸጥ ይችላል እየተባለና የውጭ ከረንሲ ለመቃረም ሲባል በአገር ውስጥ የሚመረትን ምርትም ሆነ ፍራፍሬዎች እየሟጠጡ ወደ ውጭ በመላክና መሬትን ለውጭ „እንቬሰተሮች“ በማከራየት አልነበረም በአውሮፓ ምድር ውስጥ ካፒታሊዝም ማደግ የቻለው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የካፒታሊዝም ዕድገት በውስጥ ኃይሎች ብቻ ተግባራዊ የሆን ሳይሆንን፣ ከውጭ የመጣ አስተሳሰብም ለካፒታሊዝም ዕድገት ዕምርታን ሰጥቶታል። ከውጭ የመጡ አስተሳሰቦችና ዕውቀቶች በመጠናትና ውስጣዊ ባህርይ(internalize) እንዲኖራቸው በማድረግ የካፒታሊዝምን ዕድገት ማፋጠን ተችሏል። ይህም ማለት የውጭው ባህልና የአሰራር ኖርሞች፣ እንዲሁም ከውጭ የተቀዱ የቴክኖሎጂ አሰራርና ፈጠራ የግዴታ በሰው ጭንቅላት ውስጥ እንዲቀረጹ ከፍተኛ ትግል ይደረግ ነበር። ከውጭ የሚመጡ አሰተሳሰቦች የራሳቸውን ደሴት በመስራት በራሳቸው ክልል ብቻ እንዲሽከረከሩ የሚደረጉ አልነበሩም። የአውሮፓን የካፒታሊዝም ዕድገት ለተመለከተ፣ አንደኛው አገር ከሌላው አገር እየኮረጀ ሁለ-ገብ ዕድገትን እንዳመጣ መገንዘብ እንችላለን። እንደአገራችን ዕውቀት የጋን መብራት በመሆንና የራስን ዓለም በመመስረት ከሰፊው ህዝብ ጋር ሳይገናኙ አይደለም ካፒታሊዝም በአውሮፓ ምድር ውስጥ ማደግና፣ ዓለምን መቆጣጠርና  ማዳረስ የቻለው። ካፒታሊዝም ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝና የሀብት ክምችትም በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ የቻለው ምርቶች በመመረታቸው ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛው የሚመረተው ምርት አገር ውስጥ ገበያ ላይ የመገዛትና የመሸጥ ዕድል ካገኘና፣ በዚህም አማካይነት የገንዘብ መሽከርከር በከፈተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ እንደሆን ብቻ ነው።

ገበያ በህብረተሰብ የታሪክ ዕድገት ውስጥ ግዴታ የሆነውን ያህል፣ የኋላ ኋላ በተለይም የእነ ጆን ሎክና የሌሎች ዩቲላቴሪያን አስተሳሰብ በአሸናፊነት ሲወጣ፣ ካፒታሊዝምና የግል ሀብት ተያይዘው በመውጣት በህብረተሰብ ውስጥ የመደብ አከፋፈል ግልጽ እየሆነ መጣ። የምርት መሳሪያዎችና ሌሎች ሀብቶች የሌለው የግዴታ የስራ ጉልበቱን እንዲሸጥ ተገደደ። ተቀጥሮ በመስራት ብቻ ገንዘብ በማግኘት የቀን ተቀን ፍላጎቱን ማሟላት ቻለ። አዲስ በተፈጠረውና ውስብስብ እየሆነ በመጣው ግኑኝነት መሰረት፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ኃይሎች በምርት የስራ ቦታና በገበያ የሚገናኙ ሁኑ። ገንዘብም ከዕቃ ባህርዩ(Commodity Character) በመላቀቅ እቃዎችን በፍጥነት ማሽከርከሪያ መሳሪያ በመሆን ህብርተሰብአዊ ኃይል እየሆነ መጣ። ለብዙ መቶ ዐመታት ወርቅ፣ ብርና መዳብ እንዲሁም ሌሎች ለፍጆታ ጠቀሜታ የሚያገለግሉ እንደገንዘብም በማገልገል ለገበያ ዕድገት ዕምርታን መስጠት ችለዋል። ካፒታሊዝም እያደገና እየተወሳሰበ ሲመጣ ግን እነዚህ የፍጆታ ባህርይ ያላቸው የገንዘብ ዐይነቶች እያደገ የመጣውን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም። ለዕቃዎች በሰፊው መሸከርከር የሚያመች፣ ካለብዙ ወጪ በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊሽከረከር የሚችል በመንግስት የተደገፈ የወረቀት ገንዘብ አስፈላጊ እየሆነ መጣ። ስለሆነም፣ በመንግስት የተደገፈ የወረቀት ገንዘብና ሳንቲም በብዛት በመታተም የካፒታሊዝምን ዕድገት ማፋጠን ቻሉ። የወረቀት ገንዘብ የበለጠ ተቀባይነትን እያገኘ ሲመጣም የሰው በሰው ግኑኝነትም እየተለወጠ መጣ። ገንዘብ የህበረተሰብአዊ ግኑኝነት መለኪያ ሆነ። ተራ የገበያ ኢኮኖሚ ወይም የነፃ ገበያ የሚለው አባባል አዲስ በተፈጠረው የሀብት ቁጥጥርና የህብረተሰብ ግኑኝነት አማካይነት ወደ ካፒታሊዝምነት ተለወጠ። ካፒታሊዝምም ህብረተሰብአዊ ስርዓትን መግልጫና ብዙ ነገሮችን ያካተተና የያዘ ስርዓት ለመሆን በቃ። ለዚህ ነው ማርክስም ሆነ ሹምፔተር ካፒታሊዝምን ዝም ብለው ነፃ ገበያ ወይም የገበያ ኢኮኖሚ ብለው የማይጠሩት። ምክንያቱም እንደዚህ ዐይነቱ አባባል ያልተሟላና ብዙ ነገሮችን ስለማያካትት ነው። ይህም ማለት ካፒታሊዝም ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትንም ሲገልጽ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ በገቢ አከፋፈልና ምድባ የሚገለጽና፣ አንዲሁም በህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ(Social Status) የሚታይ ህብረተሰብአዊ አወቃቀር የካፒታሊዝም አንደኛው ገጽታ መሆን ቻሉ። በሌላ ወገን ግን የእነ አዳም ስሚዙ አገላለጽ ታሪካዊ አይደለም፤ የማርክስም ሆነ የሹምፔተር እንዲሁም የሌሎች የታሪክን ዕድገት ያካተተና ካለ ምርት ኃይሎች ዕድገት(Production Forces)፣ ማለትም ካለቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊገለጽ አይችልም። በተጨማሪም የአዳም ስሚዙ የገበያ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ደግሞ የኒዎ-ክላሲካል የገበያ ኢኮኖሚ ፅንሰ-ሃሳብ ውስጣዊ ኃይል የሌለውና፣ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ የማይሸጋገር ሲሆን፣ የማርክስም ሆነ የሹምፔተሩ በዚያ ባለህበት ቆሞ የሚቀር አይደለም። ውስጥ ባለው ኃይልና ውስጣዊ ቅራኔ የአረጁ ኢንዱስትሪዎችን በማፈራረስና በተሻሉና ምርታማቸው ከፍ ባሉ ማሺኖች በመተካት አዲስ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምንና ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት እንዲፈጠር ያደርጋል። በዚህም አማካይነት የሰው ከሰው ግኑኝነት የበለጠ ገንዘባዊ እንዲሆን በማድረግና፣ ቀጥተኛ አምራቹንም የበለጠ ጥገኛ በማድረግ የሰው አስተሳሰብ በቀጥታ ከፍጆታ አጠቃቀም ጋር እንዲያያዝ ያደርጋል። ለዚህም ነው የአራት መቶ ዓመትን የካፒታሊዝምን ዕድገት በጥብቅ የተከታተለ፣ ምርት በዐይነትና በብዛት መመረቱ ብቻ ሳይሆን፣ የምርት ማምረቻ መሳሪያዎችም ምጥቀትን በማግኘት የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን ግኑኝነት መለወጥ እንዲችል የተገደደው። በቴክኖሎጂ መሻሻል የስራ ሰዓት መቀነሱ ብቻ ሳይሆን፣ ሰራተኛው ከአዲሱ ቴክኖሎጂ ጋር ለመስተካከል ሲል በፍጥነት መስራት ተገደደ። አጠቃላይና የተስፋፋ የሀብት ክምችት (Expanded  Capital Accumulation) በመዳበር ካፒታሊዝም በአገር ብቻ እንዳይወሰን ተገደደ። ቀሰ በቀስ እያለ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እየያዘ መምጣት ቻለ።

አዲሱና የተሻሻለው የቴክኖሎጂ ለውጥ አሰራር አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ የተወሰኑ በተኖችን ብቻ በመንካት የምርትን ሂደት እንዲያፋጥን አስቻለው። በዚያው መጠንም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት የሰው ኃይል ትርፍ(Redundant) እየሆነ እንደመጣ እንመለከታለን። በቴክኖሎጂዎች ምጥቀትና ውድድር አማካይነት የካፒታል ክምችትና(Concentration of Capital) የኢንዱስትሪና የባንክ ካፒታል እየተቆላለፉ በመምጣት፣ ፋይናንስ ካፒታል የኢንዱስትሪን ዕድገትና የቴክኖሎጂን ምጥቀት መወሰን ቻለ። በተጨማሪም፣ የኢንዱስትሪ ካፒታል በከፍተኛ ፍጥነት ሲያድግና የካፒታል ክምችትም እየተስፋፋ ሲመጣ፣ በአንድ በኩል መጠነኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወይም ባህላዊ የዕደ-ጥበብ ስራዎች እየተዳከሙና እየጠፉ ሊመጡ ችለዋል። ከዚህም በላይ የማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት፣ መኖርና ያለመኖር በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ውስጠ-ኃይለ የሚወሰን ሆነ። ምክንያቱም መጠነኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ተለዋዋጭ ዕቃዎችንና(Spare parts) መጠገኛዎችንም ሆነ ዋና ዋና ክፍሎችን አምራች ስለሆኑ፣ ለምሳሌ የመኪና ገበያ በሚቀዘቅዝበት ጊዜ ትናንሽ ኢንዱስትሪዎችም ይዳከማሉ ማለት ነው። ይህም የሚያመለክተው የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ርስበራሳቸው የተያያዙና(Value-added Chain)አንደኛው በሌላው ላይ የተመካና፣ የአንደኛው መዳከም ወይም መጠንከር በሌላው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው። ይሁንና ግን በዘመነ-ግሎባላይዜሽን፣ ለምሳሌ የአንድ መኪና የተለያዩ ክፍሎች እዚያው ፈጣሪው አገር ብቻ አይመረቱም። የማምረቻን ዋጋ ለመቀነስ ሲባል የተወሰነው የመገጣጠሚያ ክፍል በተለያዩ አገሮች በመመረት የመጨረሻ መጨረሻ ዋናው አምራች አገር ምርቶቹ በመገጣጠም የመጨረሻው ምርት ውጤት ገበያ ላይ ይቀርባል። ስለሆነም የዛሬው የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ደግሞ ካፒታሊዝም ከሶስት መቶና አራት መቶ ዐመት በፊት ከነበረው በብዙ መቶ እጅ ልቆ የሚገኝ ነው።

ካለምንም የጭንቅላት ማስጨነቅ ዛሬ የቴክኖሎጂዎችን ዕድገት ስንመለከትና የፍጆታ ዕቃዎችንም ስንጠቀም ሁሉም ነገር በጤናማ መልክና ካለ ውስጣዊ ቅራኔ የሚካሄድ ነው የሚመስለን። በመጀመሪያ በምዕራብ አውርፓ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የሰራተኛው መደብ መብቱን ለማስጠበቅ ሲል በሙያው ማህበሩ አማካይነት ከፍተኛ ትግል አድርጓል። የሳምንት የስራ ሰዓት ወደ 42ና ወደ 40 ሰዓት እንዲቀነስ ማድረግ፣ እንዲሁም ደግሞ በሰራተኛ ማህበርና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ በግሩፕ በመደራጀት ከከበርቴው መደብ ጋር የሚደራደር ተጠሪ መምረጥ መቻል፣ እነዚህ ሁሉ በትግል የተገኙ ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ ቴክኖሎጂዎች ምጥቀትን ባገኙ ቁጥር የሰራተኛው የመከራከርና የመደራደር ኃይል እየተዳከሙ እንደመጡ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ባለፉት ሰላሳ ዐመታት በካፒታሊዝም ዕድገት ውስጥ የታዩት አሉታዊ ክስተቶች የሰራተኛውን መደብ በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከም አድርገውታል። ትላልቅ ኩባንያዎች ትርፍ ለማካበት ሲሉ የተወሰነውን የኢንዱስትሪ ክፍል ርካሽ የስራ ጉልበት ባለበት አገር እየወሰዱ በመትከል ወደ ውስጥ ብዙ ሰራተኞች እንዲባረሩና የባህልም ውድቀት እንዲመጣ አድርገዋል። የትራዲሽናል ኢንዱስትሪዎች በግሎባላይዜሽን አማካይነት መዳከማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሌሎች አገሮች ተወስደው እንዲተከሉ በማድረግ በየአገሮች ውስጥ ከኢንዱስትሪ መስክ ጋር የተያያዙ ሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችም እንዲዳከሙ ተደርገዋል። በዚያው መጠንም በተለይም በትናንሽ ከተሞች ውስጥ በኢንዱስትሪዎች ተነቅሎ ወደ ሌሎች አገሮች መወሰድና በሰራተኛው ከስራው ቦታው መባረር የተነሳ የየአካባቢ አስተዳደሮች ከህዝብ የሚሰበስቡት ግብር(Tax) እጅግ እየቀነሰ መጥቷል። ይህ ማለት ደግሞ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ፣ ከተማዎችን ለማፅዳትና ሌሎች የማህበራዊ መስኮችን ለመደጎም የሚያስፈልገው ወጪ እየቀነሰ ሊመጣ ችሏል ማለት ነው።

በተለይም የፊናንስ ካፒታል በከፍተኛ ደረጃ ማደግና ራሱን ከኢንዱስትሪ አግልሎ በገንዝብ አማካይነት ብቻ ትርፍ ማካበት መቻል ብዙ መንግስታትን ከቁጥጥር ውጭ እያደረጋቸውና፣ በተራ የሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ የኢኮኖሚውን ዕድገት ሊቆጣጠሩና የኢኮኖሚውን መዛባትም ሊያርሙ የሚችሉበት ሁኔታ እጅግ እየጠበበ መጥቷል። የዚህ ዐይነቱ የፊናንስ ካፒታል ማደግና በተለያዩ ዐይነቶች መገለጽ፣ ለምሳሌ ሄጅ ፈንድስ ወይም ኢንቬስሜንት ካፒታል በሚባሉት መልኮች የሚሽከረከረው የፊናንስ ካፒታልና፣ ይህ ደግሞ እንደገና ከትላልቅ ባንኮች ጋር መቆላለፍ የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችንና አንዳንድ የደቡብ አውሮፓን ኢኮኖሚዎችንም ከመቆጣጠር አልፎ እያፈራረሰቸውም እንደመጣ እንመለከታለን። ለምሳሌ ግሪክን እዚህ መቀመቅ ውስጥ የከተታት ከራሷ የውስጥ ኢኮኖሚ አወቃቀር ድክመት ባሻገር የፊናንስ ካፒታል አይሎ መውጣትና በዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንድትገባ በማድረጉም ጭምር ነው። በተጨማሪም እጅግ ልፍስፍስ የሆነ የፖለቲካ ኤሊት ለፊናንስ ካፒታል አጎብዳጅ በመሆኑም ጭምር ነው። የአውሮፓው አንድነትን የአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠጋ ብሎ ለተመለከተ የባሰውን የግሪክን ኢኮኖሚ ያደከመና የባሰ የውስጥ ካፒታል ወደ ውጭ እንዲወጣ ያገዘ ነው። ግሪክ ከፋይናንስ ገበያ ላይ የምትበደረው ተጨማሪ ብድር ወይም ከአውሮፓ አንድነት የምታገኘው ብድር የጀርመንንና የፈረንሳይ ባንኮችን ከኪሳራ ለማዳን የሚውል ነው። በዚህ መልክ ብዙ አገሮች መቀመቅ ውስጥ እንዲገቡና እንዲራቆቱ ሆነዋል። ለብዙ ዐመታት ዕዳው በወለድ-ወለድ(Compound Interset) አማካይነት የተነሳ በማደጉ ለብዙ ዓመታት ዕዳ ከፋይና ንፁህ ካፒታልን ወደ ውጭ እንዲያወጡ ተገደዋል። ይህ በራሱ ደግሞ ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውንና ህብረተሰብአቸውን በስርዓት እንዳያውቅሩና እንዳያደራጁ አግዶአቸዋል።

ይህ የካፒታሊዝም አንደኛው ገጽታ ሲሆን፣ በምርት አማካይነት በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተስፋፋው የምርት ክንውን ለእነዚህ አገሮች በምንም ዐይነት ዕድገትንና ስልጣኔን ሊያጎናጽፋቸው አልቻለም። ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የካፒታሊዝምን መስፋፋት ስንመለከት ዋናው ዓላማው ስልጣኔና እንዲሁም ደግሞ ሳይንስንና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ሳይሆን፣ የጥሬ ሀብትን መዝረፍና ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች እንዲጫን ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ በተወሰኑ መስኮች ላይ ብቻ መረባረብ ሲሆን፣ እንዲዚህ ዐይነቱ በጥሬ ሀብት ማውጣት ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ የሀብት ዘረፋ በማካሄድ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ አግዷል። ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልና፣ ከተማዎች ካለምንም ዕቅድ መሰራትና መቆሽሽ የብዙ አፍሪካ አገሮች ዕጣ ሆኗል ማለት ይቻላል። በዚያው መጠንም እንዲዚህ ዐይነቱ የግሎባል ካፒታሊዝም መስፋፋት በአፍሪካ ምድር ውስጥ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ እንዳይዳብርና እንዳይስፋፋ አግዷል። በየአገሮች ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ እንዲካሄዱ መደረጉ ደግሞ ከገጠር ወደ ጥቂት ከተማዎች ውስጥ የሰውን ፍሰት በማስከተል፣ ከተማዎች የዕድገትና የብልጽግና ቦታዎች ከመሆን ይልቅ በጣም ጥቂት ሀብታምና፣ ሰፋ ያለ ደሃ ፊት ለፊት የሚፋጠጡበት መድረክ በመሆን ህብረተሰብአዊና  ማህበራዊ ቀውስ በማስከተል የህብረተሰብና የህብረ-ብሄር ትርጉም እንዲወድሙ ተደርገዋል።

በዚህም የተነሳ ከኢንዱስትሪ አገሮች እየተነቀሉ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች ከውስጥ ዕውነተኛ ሀብት ፈጣሪዎች ያልሆኑና ህዝቡም ቴክኖሎጂን እንዳይማር ያገዱና የሚያግዱ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢንዱስትሪዎቹ በትላልቅ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ያሉና ከላይም የሚቀመጡ ማኔጀሮች የራሳቸው ነፃነት የሌላቸው ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ቴክኖሎጂዎቹ ከምርምርና ከዕድገት ጋር የተያያዙ አይደሉም። ቀጥታ ግኑኝነታቸው ከእናት አገሮቻቸው ጋር ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ የሚመረቱት ምርቶች ለዓለም ገበያ ተብለው ስለሆነ ወደ ውስጥ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ለገበያው ማደግና መስፋፋት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በአራተኛ ደረጃ፣ በየፋብሪካው ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ደሞዙ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ሰራተኛው ምርቶችን ገዝቶ የመጠቀም ኃይሉ በጣም አነስተኛ ነው። በአምስተኛ ደረጃ፣ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች ከየአገሩ ባንክ ጋር ምንም ግኑኝነት የላቸውም። ይህ ማለት ደግሞ የገንዘብን በፍጥነት መሽከርከርና ህብረተሰብአዊ ኃይል ማግኘት በከፍተኛ ደረጃ ያግደዋል ማለት ነው። በኢንዱስትሪና በባንክ ማሀከል ግኑኝነት ሲኖር ብቻ ነው የገበያ ኢኮኖሚ ማደግ የሚችለው። በስድስተኛ ደረጃ፣ የሰራተኞችንና የስራ ቦታዎችን ሁኔታ ለተመለከተ፣ ሰራተኞች እጅግ በአሰቃቂ ሁኔታ ነው የሚሰሩት። የምንለብሳቸው ጂንሶችና የምንጠቀምባቸው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በሙሉ በርካሽ ጉልበት የተመረቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ብዙ ወጣት ሴቶች ጤንነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየተቃወሰ የሚመረቱ ምርቶች ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰላሳና በአርባ ዕድሜያቸው በጤንነት መቃወስ የተነሳ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። ኑሮን ሳይኖሩ ይሞታሉ። ብዙዎችም የአልጋ ቁራኛ በመሆን ፍዳቸውን ያያሉ። ይህንን ነው እንግዲህ የዛሬው ካፒታሊዝም የሚመስለውና፣ በአገራችን ደግሞ ዘመኑ የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው እየተባለ የሚወደስለትና ካለቡዙ ቅራኔዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይስፋፋ ይመስል የሚነዛው። ብዙዎች ካለማወቅ በሚያናፍሱት ወሬና በፊናንስ ካፒታል ግዳጅ በሚያካሂዱት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የተነሳ የብዙ መቶ ሚሊዮኖች ህዝብ እየተረበሸና ጤናማና ለስልጣኔ የሚያመች ረጋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡ እየታገዱ ነው። የአንድ ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን የሶስትና የአራት ትውልድ ዕድል የሚበላሽበት ሁኔታ ዛሬ ተነጥፏል ማለት ይቻላል። ዛሬ በአገራችን ምድር ውስጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጡትና እነሱ የሚሉትን የገበያ ኢኮኖሚ የሚያራምዱ በነሱ ባልበሰለ ሁኔታ በሚካሄድ ፖሊሲ አማካይነት የተፈጸመውና የሚፈጸመው ወንጀል የማይታያቸው ይህንን የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ቅራኔና ሂደት በቅጡ ካለመራዳት የተነሳ ነው። አላዋቂ ሳሚ … እንደሚሉት አነጋገር።

ውድድርንና  የካፒታሊዝም ዕድገት !

የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም እንደ አገራችን በተራ ነጣቂነት ወይም ዐይን ባወጣ ዘራፊነት የሚደነገግና ውስጠ-ኃይል የሚያገኝ አይደለም። ማርክስ እንደሚለውና በትክክልም እንደሚረጋገጠው ውድድር(Competition) የካፒታሊዝም ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀትም የሚታየው በውድድር አማካይነት ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ምርምርና ፈጠራ እየታገዙ ማምረት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ በገበያ ላይ ምርት እያመረተ የሚያቀርብ ካፒታሊስት ተወዳዳሪውን በመርዝ ወይንም በአንዳች ነገር ህይወቱን ለማጥፋት ወይም ለመግደል ተንኮል የሚያብሰለስል ሳይሆን፣ በምን መንገድና እንዴት አድርጌ ምርት ባመርት ተወዳዳሪዬን ለማሸነፍ እችላለሁ፣ ወይም የበለጠ የገበያ ድርሻ ይኖረኛል ብሎ ታጥቆ በመነሳት የእንቬስትሜንት ስትራቴጂውን ይቀይሳል። ከዋጋ አንፃር የማምረቻ ዋጋን በመቀነስና ምርትን በነፍስ ወከፍ ሲተመን በማሳደግ(Productivity)፣ እንዲሁም ደግሞ ምርቱ ጥራት እንዲኖረው በማድረግ ብቃትነቱን በማሳየት በገበያ ውስጥ ለመቆየት ጥረት ያደርጋል። በየጊዜው የምርቱን ሁኔታ ይለዋውጣል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት የተወሰነ ምርት፣ መኪና ወይም ማቀዝቀዣ የተወሰነ የፍጆታ ዘመን ነው ያላቸው። በመጀመሪያው ወቅት አዲስ ምርት ገበያ ላይ ሲወጣ እንደብርቅ ይታያል። ቀስ በቀስም ሰው እየለመደው ሲሄድ ገዝቶ ይጠቀማል። በገበያ ላይ የመሸጡ ኃይል እያደገ ይመጣል። ሌላው ተመሳሳይ ምርት የሚያመርት ካፒታሊስት ውበቱንና የአጠቃቀሙን ዘዴ በመለወጥ ተመሳሳይና የተሻሻለ ምርት ለገበያ ያቀርባል። የድሮውም ምርት ገበያ ላይ ተገዢነቱ እየቀነሰ በመምጣት ከገበያ ላይ እየተስፈናጠረ ይወጣል። በዚህ መልክ በስድሳኛውና በሰባኛው ዓ.ም ይመረቱ የነበሩ መኪናዎችም ሆነ ማቀዝቀዣዎች ዛሬ ገበያ ላይ በፍጹም አይገኙም። በተጨማሪም የኃይልን አጠቃቀምና የአካባቢን ብክለት ለመቀነስ ሲባል በተለይም የረዥም ጊዜ ዕድሜ ያላቸው ምርቶች በጥራትም ሆነ በአጠቃቀም ደረጃ እጅግ እየተሻሻሉና ለምቾትም አጋዥ እየሆኑ መጥተዋል።

ውድድር ለካፒታሊዝም ዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን ያህልና፣ የገበያ ኢኮኖሚ የሚለው ተራ አነጋገር በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ያህል፣ ይህ ዐይነቱ በውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ ከህግ ውጭ የሚሰራ ነው ማለት አይደለም። በአምራችና በነጋዴ መሀከል ያለው ግኑኝነት በአንድ ወገን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በነጋዴውና በተጠቃሚው መሀከል ያለው ግኑኝነት በህግ ላይ ተመርኩዞ የሚንቀሳቀስ ነው። በመጀመሪያ አምራቹ ካለምንም ማጭበርበር ምርቱን አምርቶ ለነጋዴው ያቀርባል። ነጋዴው በአምራቹ ላይ ሙሉ ዕምነት አለው ማለት ነው። የሚያጭበረብር አምራችና ነጋዴ በህግ ተጠያቂዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ምናልባት በምርቱ አጠቃቀም ላይ የተወሰነ ኖርምን ተከትሎ ያልተሰራ ምርት አደጋ የሚያደርስ ከሆነ አምራቹ እንደ አደጋው ዐይነት ፈቃዱን እስከመነጠቅ ይደርሳል። ይህ ዐይነቱ ህግ ጠቅላላውን የገበያ ሂደት የሚመለከትና ብዙ ነገሮችን የሚያካትት ነው። ከዚህም በላይ በአለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት ተጠቃሚው በዕውቀት እየዳበረ ሰለመጣና፣ የተጠቃሚዎችም ማዕከል(Consumer Protection Agency) ወይም ድርጅት ስላለ፣ ተጠቃሚው በምርት አጠቃቀም ምክንያት የተነሳ የሚደርስበት ጉዳትም ሆነ ያልተስተካከለ አጠቃቀም ዘዴ አቤቱታ ሊያሰማና ሊከስም ይችላል። ይህም ማለት በአገራችን በዘልማድ አነጋገር እንደሚናፈሰውና እንደሚሰራበት ልቅ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሳይሆን፣ የምዕራቡ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓትን ይዞ የሚጓዝና በጣም የተወሳሰበ ነው። ከዚህም በላይ በስርዓቱ ውስጠ-ኃይልነትና የሰዎችም የፈጠራ ችሎታ የተነሳ ከአንድ ዐይነት ነገር የተለያዩ ብዙ ነገሮችን ማምርት ይችላል። ለምሳሌ ከእንጨት፣ እንደ ባህርይው ከልጆች መጫዎቻ አንስቶ  የተለያዩና የሚያማምሩ መቀመጫዎችና ወንበሮች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ነገሮች ማምረት ይቻላል። እንዲሁም ከተለያዩ የፍራፍሬ ወይም ጥራጥሬ ነገሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ለመቀቀያና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያገለግሉ በመጭመቅ ዘይት ማምረት ይቻላል። እንደ አገራችን በካፒታሊስት አገሮች ኑግን፣ ተልባን፣ ሰሊጥን፣ ሱፍንና ሌሎች ነገሮችን የውጭ ከረንሲ ለመቃረም ሲባል እስከነነፍሳቸው የመላክ ባህል የለም። ይህንን የሚያደርግ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ምንነትና በኢንዱስትሪዎች መሀከል ስለሚኖረው ውስጣዊ ግኑኝነትና የሀብት ክምችት ምንጭነት የማያውቅ መሆን አለበት። እንደዚህ የሚያደርግ መንግስት በዚያውም መጠንም የውስጥ ገበያ እንዳያድግና ኢኮኖሚው እንዳይተሳሰር ሳያውቀው ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ነጋዴው እዚያው ቀጭጮ እንዲቀር ያደርገዋል፤ የስራ መስክ እንዳይከፈት ያደርጋል። በዚህም የተነሳ ሰፊው ህዝብ ምንም ገቢ ስለማያገኝ ወደ አልባሌ ስራዎች ላይ ይሰማራልል። ይህም ማለት እንደሰውነታችን መተሳሰር ያለበትና እንደደማችን በሰውነታችን ውስጥ መሽከርከር የሚኖርበት ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ህግን ካለማወቅ የተነሳ በአንድ አገር ውስጥ ሁለንታዊ ዕድገት እንዳይኖር ይደረጋል። በአጠቃላይም ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣ መንገዱን ሁሉ ያፍናል። የህዝቡን የፈጠራ ስራ ከማፈኑም በላይ ኑሮው የተዘበራረቀ እንዲሆን ያደርጋል።

ስለዚህም ስለውድድር በምናወራበት ጊዜ የኢኮኖሚው ኤጀንቶችን የፈጠራ ችሎታና በየጊዜው እንደገበያው መለዋወጥ ከሁኔታው ጋር ሊኖር የሚችለውን መጣጣምና በፍጥነት መጓዝ ማጤን ያስፈልጋል። በዚህ ላይ ለውድድሩ መጧጧፍ የጊዜ ኢኮኖሚና ቦታ(Time &Space) ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። አንድን ዕቃ አምርቶ ወደ ሌላ ቦታ በፍጥነት ለማድረስ ፈጣንና በቀላሉ አደጋ ሊያደርስ የማይችል የትራንስፖርቴሽን ማገልገያ ያስፍልጋል። እንደዚሁም በመርከብ፣ በባቡርና በመኪና ሊጫኑ የሚችሉ ዕቃዎችን መለያየት ያስፈልጋል። ጤናማና ጥንቃቄ የተሞላበት የማከማቻ ቦታ ለዕቃዎች መከማችትና ለረዥም ጊዜ መቆየት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ወደ ቦታ ስንመጣ ይህ ዐይነቱ አገላለጽ በደንብ ከተደራጀ ገበያና መደብር ጋር የተያያዘ ነው። በሚያማምሩ ከተማዎችና መንደሮች የሚገለጽ ነው። ስርዓት ያለው የቤት አሰራርና የተለያዩ ተግባር ያላቸውን ቤቶችና አዳራሾች የሚመለከት ነው። የገበያ አዳራሾች ውብና ሰፋ ብለው እንዲሁም ማራኪ ሆነው መሰራት አለባቸው። በዘመኑ ሁኔታ ደግሞ ከመናፈሻና ከልጆች መጫዎቻዎች እንዲሁም በአካባቢው ማራኪ ከሆኑና ሰውን ከሚጋብዙ ቡና ቤቶች፣ የቲያትርና የሲኒማ እንዲሁም ልዩ ልዩ የመዝናኛ ቦታዎች ጋር የመሰራትንና የመዘጋጀትን እንዲሁም መያያዝን ጉዳይ ይጠይቃል። በዚህ መልክ የሚዘጋጅና በአካባቢው አንድ ወጥ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የምርት ዐይነቶች ተደራጀተው የሚገኙ ከሆነ ለገበያው ዕድገትና ለውድድር ከፍተኛ ዕምርታን ይሰጣል ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር የሚነዛው ስለገበያ ኢኮኖሚ ሳይንሳዊ ባህርይ የሌለው በተራ ችርቻሮ ላይ የተመረኮዘና ተዋንያኖችን የበለጠ የሚያንቀዠቅዥና አጭበርባሪ የሚያደርጋቸው ነው። ወያኔዎችና አማካሪዎቻቸው  እንደዚህ ዐይነቱን ኢኮኖሚ ነው አንዳንዴ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እያሉ ነበር የሚነግሩን። አልፎ አልፎ ደግሞ የለም እኛ ኒዎ-ሊበራሊዝምን የምንዋጋና በመንግስት የተደገፈ(Developmental State) የኢኮኖሚ ፖሊሲን ነው የምንከተለው እያሉ ነበር እዚያው በዚያው የሚያላግጡብንና ግራ ለማጋባት ይሞክሩ የነበረው። ይህም  የሚያመለክተው የገዢው መደብና ተከታዮቹ የቱን ያህል በህዝብ ላይ እንደሚያላግጡ ነው።

ከዚህ ባሻገር ተመሳሳይ ምርት በሚያመርቱ ካፒታሊስቶች መሀከል የሚካሄደው ውድድር በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። እንደሚታወቀው የካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋት በምርት ክንውን ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ የፍጆታ አጠቃቀሞች፣ የፊናንስ ግኑኝነትና ደካማ አገሮችን በዕዳ መተብተብ አጠቃላዩ የካፒታሊዝም የሀብት ማካበቻ ዘዴዎችና፣ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ሀብት ከሶስተኛው ዓለም አገሮች ወደ ካፒታሊስት አገሮች የሚተላለፍበት የብዝበዛና የድህነት መፈልፈያ መሳሪያም ነው። ይህም ማለት በአገር ውስጥ የሚካሄደው የካፒታሊዝም የሀብት ክምችትና ዘዴ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ የሚመካ አይደለም። እያንዳንዱ የካፒታሊስት አገር ህብረተሰቡ ገዝቶ ከሚጠቀመው በላይ ስለሚያመርት ትርፍ ምርቱን ለመሸጥ ሲል የውጭ ገበያ ያስፈልገዋል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በተለያዩ አገሮች መሀከል ባሉ ካፒታሊስቶች ዘንድ የግዴታ ውድድር ይፈጥራል። የተለያዩ ካፒታሊስት አገሮች ምርቶቻቸውን፣ ለምሳሌ መኪና ወይም የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በዓለም ገበያ ላይ ለመሸጥ ይችሉ ዘንድ በተቻለ መጠን ለምርት የሚያወጡትን ወጪ እንዲቀንሱ ይገደዳሉ። በሌላ ወገን ደግሞ አንዳንድ ምርቶች የውጭ ገበያ ላይ ለመሸጥ እንዲችሉ መንግስታት ከኤክስፖርት ቀረጥ ነፃ ያደርጉላቸዋል። የማምረቻን ዋጋ እንደልባቸው አገር ውስጥ መቀነስ ስለማይችሉ፣ ለምሳሌ የሰራተኛውን ደሞዝ በመቀነስ፣ የተለያዩ አካሎች(Spare parts) ሌሎች የሰራተኛ ደሞዝ ርካሽ የሆኑ ሌሎች አገሮች ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ ምርቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ። ስለዚህም የዛሬው ካፒታሊዝም ከሁለት መቶ ዐመት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጅ ይለያል። ውድድሩ በትናንሽ ካፒታሊስቶች መሀከል የሚደረግ መሆኑ ቀርቶ የዓለምን ገበያ ለመቆጣጠር በሚሽቀዳደሙ ጥቂት ያበጡ ካፒታሊስቶች(Oligopolies) በመሆን የዓለም ገበያ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት፣ የሶስተኛው ዓለም አገር ኢኮኖሚዎችም እየተዘበራረቁ ሊመጡ ችለዋል። ይህ ዐይነቱ በተወሳሰበ የአደራጃጀትና የአመራረት ስልት የሚንቀሳቀስ የምርት ክንውን እንዲያው በተራ የነፃ ገበያ ሊገለጽ የሚችል አይደለም።

ከዚህም በላይ፣ የዛሬው ዓለምን የሚቆጣጠረው ካፒታሊዝም የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የጥሬ-ሀብት በመቆጣጠርና የሰውን ጉልበት በመብዘብዝ ነው በመጀመሪያ ደረጃ ጥንታዊ የሀብት ክምችትን(Primitive Capitalist Accumulation) ማዘጋጀትና ለኢንዱስትሪ አብዮት መጠቀሚያ ማድረግ የቻለው። በመጀመሪያ ደረጃ በባሪያ ንግድ የተነሳ ወደ አውሮፓና ላቲን አሜሪካ፣ በኋላ ደግሞ ወደ ኃያሉ አሜሪካ የተሸጡ አፍሪካውያን በፕላንቴሼን ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሰማሩና እንዲሰሩ በመገደድ ለካፒታሊዝም የሀብት ክምችትና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በቅኝ ግዛት አማካይነትና አዲስ በተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የስራ-ክፍፍል አማካይነት ብዙዎቹ የአፍሪካ፣ የላቲንና የሴንትራል አሜሪካ አገሮች የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት አምራቾች እንዲደረጉ በመገደድ የኢንዱስትሪ አገሮችን ህዝቦች በርካሽ ዋጋ መመገብ ብቻ ሳይሆን፣ ለጠቅላላው የሀብት ክምችት ከፈተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ዛሬም ቢሆን አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ከሶስተኛው ዓለም አገሮች በሚመጡ የጥሬ-ሀብቶችና የእርሻ ምርት ውጤቶች የሚመኩና፣ ይህ ሁኔታም እንዳይቀየር የተለያዩ ተቋማትን በመፍጠር ዕድገታቸውን የሚቆጣጠሩ ናቸው። ከዚህ ስንነሳ ይህ ነፃ ገበያ እየተባለ የሚጠራው የካፒታሊዝም የምርት ክንውን እስከዚህም ድረስ ነፃ እንዳልሆነ መረዳቱ ከባድ አይደለም።

ካፒታሊዝም፣ ሳይንስና እንዲሁም ቴክኖሎጂ !

የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አብዛኛውን ጊዜ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ሲጽፉና ሲያወሩ በተለይም ሳይንስና ቴክኖሎጂ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያላቸውንና የሚኖራቸውን ሚና ቁጥር ውስጥ ባለማስገባት ነው። የኢንዱስትሪ አብዮት ከተጀመረና ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ሲመጣ፣ ኢኮኖሚ በሁሉም አቅጣጫ ሊስፋፋና ስር ሊሰድ የቻለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ መደገፍ ከጀመረ በኋላ ነው። ከባቡር ሃዲድ መሰራትና ጥራትን እያገኘ መጥቶ ፍጥነቱ ከቀድሞው ጋር ሲወዳደር በከፍተኛ ደረጃ መጨመር፣ የአይሮፕላን ስራና እየረቀቀ መጥቶ የዓለምን ህዝብ ማገናኘት መቻል፣ ዛሬ የምንገናኝባቸው የኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች… ወዘተ፣ እነዚህ ሁሉ ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የምርት ዕድገትና ጥራት፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ናቸው። በተፈጥሮ ውስጥ የሚከሰቱትን በሽታዎችና ቫይረሶች ሁሉ መዋጋትና መቋቋም የሚቻለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ ሳይንሳዊ ምርምርንና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ቦታ የማይሰጥ ህብረተሰብ በተራ የነፃ ገበያ አማካይነት ብቻ የትም ሊደርስ በፍጹም አይችልም። ዕጣው ድህነትና ረሃቭ፣ የመጨረሻ መጨረሻ እንደ አገርና እንደ ህብረተሰብ አለመኖር ይሆናል። እስከዛሬ ድረስ ቀድመው የተነሱ ስልጣኔዎች የመጨረሻ መጨረሻ ሊፈራርሱና የታሪክ ትዝታ ሆነው መቅረት የቻሉት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት ባለመቻላቸው ነው። ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ጊዜ የግዴታ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል። ካፒታሊዝም እንበለው ሌላ ስርዓት የግዴታ በሳይንስና በቴክኖሎጂ መደገፍ አለባቸው።

በመጀመሪያ ደረጃ ሳይንስ መዳበር የቻለው በታላላቅ ተመራማሪዎች፣ በአስራአምስተኛው፣ በአስራስድስተኛውና በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ሲሆን፣ ወደ ቴክኖሎጂ ማፍለቂያነትና ወደ ተግባራዊነት እየተለወጠ ሊመጣ የቻለው ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ሳይንሳዊ ግኝት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊነትና ቴክኖሎጂዎችን ፈጥሮ ወደ ምርት ማምረቻ መሳሪያነት መለወጥ የታቸለው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ምርት በዕውቅ መመረትና ምርትን ማሳደግና እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችን ማምረት የተቻለውና፣ ቀስ በቀስም ዛሬ ለማየት የበቃነውን ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀት ማየት የቻልነው። በአንዳንዶች አባባል ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው በቴክኖሎጂ አማካይነት ተፈጥሮን እስከተወሰነ ደረጃ መቆጣጠርና በተፍጥሮ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ነገሮችን በልዩ መሳሪያዎች መመርመርና ማየት የተቻለው። ስለሆነም ሰለ ገበያ ኢኮኖሚ ወይም ስለ ካፒታሊዝም በምናወራብት ጊዜ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ደግሞ በየጊዜው ከሚካሄድ ፈጠራ(Innovation) ውጭ ማየትና ማተት ስህተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ነው። ስለሆነም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በከፍተኛ የሳይንስና የቴኮኖሎጂ (A Science and Technology Driven Economic Development)  መሰረት ላይ በመመርኮዝ የሚንቀሳቀስና፣ ከተወሰኑ ዐመታት በኋላ ደግሞ አሮጌው ከገበያው በመውጣት በአዲስ የሚተካበት ልዩ ዐይነት ኢኮኖሚያዊ ክንውን ነው። ስለሆነም ነው ታላቁ የአውስትሪያው ኢኮኖሚስትና የሶሻል ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ሹምፔተር በካፒታሊዝም ዕድገት ውስጥ የሚፈጠረውንና ተግባራዊ የሚሆነውን ቴክኖሎጂ ክሪአቲቭ ዲስትራክሽን(Creative Destruction) ብሎ የሚጠራው።

የሳንይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት በተለይም በካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ ለምን ከፍተኛ ትርጉም ሊሰጠው ቻለ? በእርግጥስ የነፃ ገበያ በራሱ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት አመቺ ነው ወይ ? የሳይንስና የቴኖሎጂ ዕድገት የብዙ መቶ ዐመታት ወይም ሺህ ዐመታት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ ለአውሮፓው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት በተለይም፣ የግብጽ ስልጣኔ፣ የባቢሎናውያን፣ የግሪክ፣ ቀጥሎም ቻይናዎች በበኩላቸው አስተዋፅዖ አድርገዋል ማለት ይቻላል። በመሰረቱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምርምር የየግለሰቦች ጥረት ሲሆን፣ ከብዙ ትግል፣ ውጣና ውረድ በኋላ ነው ተቀባይነትን እያገኘ መምጣት የቻለው። የኢንዱስትሪ አብዮት እየተስፋፋና ስር እየሰደደ ሲመጣ  የከበርቴውም መደብ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ተፅዕኖ በማድረግ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምርምር ኢንስቱትሽናላዊ መሆን ጀመሩ። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታና፣ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ በቀጥታ መሳተፍና አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ  ምርምርና ምጥቀት አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል ማለት ይቻላል። በቀጥታ በመንግስት የሚደገፉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምርምር አካዳሚዎች በግለሰብ ካፒታሊሶች ብቻ ሊካሄዱ ወይም በገንዘብ ሊደጎሙ የሚችሉ አልነበሩም። ስለሆነም፣ በአንድ በኩል አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችን የምርምርና የቴክኖሎጂ ማፍለቂያ መድረክ በማድረግ ከኢንዱስትሪዎች ጋር እየተባበሩ እንዲሰሩ ማድረግ፣ በሌላው ወገን ደግሞ በቀጥታ በመንግስት የሚደገፉ ኢንስቲቱሽኖችን በማቋቋም ባጀት በመመደብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲፈጠሩና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ለካፒታሊዝም ዕድገት ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥቶታል ማለት ይቻላል። አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች እያደጉና ራሳቸውን እየቻሉ ሲመጡ ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ ትላልቅ ኩባንያዎች የየራሳቸውን የምርምር ጣቢያ በመክፈትና በመደገፍ በቀጥታ ቲክኖሎጂን ለምርት ዕድገትና ጥራት ማምረቻ መጠቀሚያ መሳሪያ ማድረግ ችለዋል። ከዚህ አጠቃላይና አጠር መጠን ያለ ትንተና ስንነሳ የነፃ ገበያ መኖር በራሱ ለቴክኖሎጂ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር በፍጹም አይችልም። የቴክኖሎጂ ዕድገትና ምጥቀት ትርጉም ሊኖራቸውና ተግባራዊ መሆን የሚችሉት ኢንስቲቱሽናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መንግስታዊ፣ ባህላዊና ህብረተሰብአዊ አመቺ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ነው። ቶሎ ቶሎ ገንዘብ ለማግኘት ጥድፊያ በሚደረግበት እንደኛ ባለ አገር፣ ሁሉም ነገር ተዘበራርቆ በሚገኝበት፣ መንግስትና ቢሮክራሲው ሳይንሳዊ ምርምርንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ዐይነተኛ ቦታንና ትርጉምን በማይሰጡበትና በማይረዱበት አገር ውስጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አብዮትን ለማካሄድ በጣም ያስቸግራል።

ያም ሆነ ይህ፣ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት ከተራ የኢኮኖሚ ስሌት አንፃር ማየቱ ብቻ ከፍተኛ ስህተት ነው። ይህ ዐይነቱ ውስን አመለካከት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአንድ ህብረተሰብ አጠቃላይ ሁኔታ፣ ደህንነትና አደጋ መከላከል ያላቸውን ሰፋ ያለ ትርጉም እንዳንረዳ ያግዱናል። ሳይንስና ቴክኖሎጂ በቀጥታ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን የፍጆታ ዕቃዎች ለማምረት የሚያገለግሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከአደጋ የሚከላከሉንን፣ ለምሳሌ እንደ እሳት አደጋ መኪና፣ ውሃ ሲሞላ መምጠጫና ሰውን በቀላሉ ማዳኛ፣ ልዩ ልዩ ለመንገድ ስራ የሚያገለግሉ መኪናዎችንና መዳመጫዎች፣ እንዲሁም አፈር ዛቂዎች፣ ዲንጋይ ተሽካሚዎች፣ በሀይድሮሊክስ እየታገዙ ከባድ ከባድ እቃዎችን ማንሳትና፣ በተለይም በገደላማ ቦታ ድልድይን መስራት የሚቻለው የሳይንስን ትርጉም የተረዳን ከሆነ ብቻ ነው።  ከዚህም በተጨማሪ፣ ዘመናዊ የህክምና መስሪያ መሳሪያዎችን፣ መድሀኒቶችንና ልዩ ልዩ ለሰው ልጅ ሊያገለግሉና ከአደጋም ሊከላከሉ የሚችሉትን መሳሪያዎች መስራት የሚቻለው፣ በተለይም የፊዝክስንና የኬሚስትሪን ህግና ምስጢር የተረዳን ከሆን ብቻ ነው። ስለዚህም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ወይም ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ ስለህብረተሰብና ስለሁለ-ገብ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በሚወራበት ጊዜ የግዴታ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ኢኮኖሚው በአስራአንድ በመቶ አድጓል፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እያካሄድን ነው የሚለው ተራ አባባል ሳይንሳዊ መሰረት የለውም። ይህ ዐይነቱ አነጋገር የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎቻችንን ስለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚህ ዐይነቱ የሽቃዮች ኢኮኖሚ የቱን ያህል በሚሊዮን የሚቆጠረውን ታዳጊ ወጣት አእምሮውን እንዳበላሸውና እንደሚያበላሽው መረዳቱ ከባድ አይሆንም። እንደዚህ ዐይነቱ ግራ መጋባትና አላዋቂነት የፈረንጆች መጫወቻ፣ መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆን አድርጎናል። የተለያዩ ግን ደግሞ ሳይንሳዊ ይዘት የሌላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባሉ ነገሮች ተግባራዊ በመሆን ከፍተኛ የሆነ የውንብድና ስርዓት ተዘርግቷል። ድህነት ተስፋፍቷል። ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሳይሆን፣ ገንዘብ ከዚህና ከዚያ በመቃረምና ትላልቅ ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሌላቸው ሆቴል ቤቶችና ቡና ቤቶች በመስራት ውድ እናት አገራችን ወደ አስረሽ ምችውነት ተለውጣች።

ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ የሀብት ክምችትና ካፒታሊዝም !

አብዛኛውን ጊዜ በአገራችን ምደር ኢኮኖሚው ይህን ያህል በመቶ አድጓል ሲባል ከስሌት ውስጥ የማይገቡ ብዙ መሰረታዊ ነገሮች አሉ። ይህ ጉዳይ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውንም አስተሳሰቡን እንዲዛባ አድርጎታል ብል እንደተራ ውንጀላ አይቆጠርብኝም። ስለ ካፒታሊዝም ዕውነተኛ ዕደገት በደንብ ሳንመረምር በተራ የጂዲፒ(GDP) አሰላል የሚቀርበው ኢኮኖሚው አደገ አላደገም እያሉ መከራከር የካፒታሊዝምን ዐይነተኛ ባህርይና ውስጠ-ኃይል ከግንዛቤ ውስጥ ካለማስገባት ጋር የተያያዘ ነው።

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ካፒታሊዝም ካለ ንፁህ ውድድርና የቴክኖሎጂ ምጥቀት እንዲሁም ደግሞ ተከታታይነት ከሌለው የሳይንስና የምርምር ውጤት ውጭ በፍጹም ሊዳብርና ሊያድግ በፍጹም አይችልም። ከዚህ በተረፈ ግን ስለካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ሌላ እጅግ አስፈላጊ መሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎችም አሉ። ይኸውም ማርክስ ክፍል አንድና(Department I) ክፍል ሁለት(Department II) እያለ የሚጠራቸው የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ መሳሪያዎች ወይም ማሽኖች ናቸው። ይህንን የማርክስን፣ የሹምፔተርንና የሎነርጋንን የዕድገት ኢኮኖሚ አሰላል ወደ ሶስትና አራት ክፍሎችም ማስፋፋት ይቻላል። ለምሳሌ ጥሬ ሀብቶችን የሚያጣሩና ወደ መጀመሪያው የምርት ክንውን የሚለውጡ ኢንዱስትሪዎች፣ ወይም ደግሞ ልዩ ዐይነት የቅንጦት ምርቶችን የሚያመርቱ እያልን ልናስፋፋው እንችላለን። በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎችን ዲዛይን የሚያደርጉና ለምርት ክንውን እንዲሆን የሚያቀርቡ ዘርፎችን ልናክልበት እንችላለን። አንባቢን ግራ ላለማጋባት በሁለቱ ክፍሎች(Departments) ብቻ ላይ ማትኮሩ ነገሮችን ለመረዳት ቀላል ይሆናል።

ማርክስ እንደሚያስተምረውና በትክክልም እንደሚያብራራው ክፍል አንድ(Department I) ብሎ በሚጠራው  ውስጥ የምርት ማምረቻ መሳሪያዎች ይመረታሉ። ማሽኖች ማለት ነው። እነዚህ ቀደም ብለው በኢንጂነሪግ ዴፓርትሜንት ዲዛይን ይሆናሉ። ለምርት ማምርቻ እንዲያገልግሉ ሆነው ይቀረጻሉ፤ ይዘጋጃሉ ማለት ነው። በዚህ ዴፓርትሜንት አማካይነት ነው የፍጆታ ዕቃ አምራቾች አስፈላጊው የምርት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ተዘጋጅቶ የሚቀርብላቸው። በሁለተኛው ክፍል ወይም ዴፓርትሜንት ሁለት እየተባለ በሚታወቀው ውስጥ የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች፣ ከረዥም ጊዜ እስከ አጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸው የተለያዩ ምርቶች ይመረታሉ።  መኪናዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ልብስና ጫማ፣ የልጆች መጫዎቻዎችና እንዲሁም ምግብና መጠጥ በክፍል ሁለት ውስጥ ነው የሚመረቱት። በሁለቱ ዴፓርትሜንቶች መሀከል ዲያሌክታዊ ግኑኝነት አለ ማለት ነው። አንደኛው ካለሌላው በፍጹም ሊያድግና ሊንቀሳቀስ አይችልም።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው?  የምርት ማምረቻው ክፍል በተከታታይ እንዲያመርት የግዴታ በፍጆታ ምርት ማምረቻ ተሰማርቶ የሚንቀሳቀስ ውስጠ-ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ የካፒታሊስት መደብ መኖር አለበት። በዴፓርትሜንት ሁለት የምርት መሳሪያዎች ሲገዛ በባንክ አማካይነት አካውንቱ ላይ ለዴፓርትሜንት አንድ ገንዘብ ይተላለፍለታል። በዚህ አማካይነት በሁለቱ ክፍሎችና(Departments) በባንክ መሀከል የሶስትዮሽ ግኑኝነት ይፈጠራል። ይህ ልዩ ግኑኝነት ለባንኮች መጠናከርና ለገንዘብ በፍጥነት መሽከርከር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ አንደኛው ጉዳይ ሲሆን፣ በምርት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ በሚያገኘው ገቢ በክፍል ሁለት የሚመረቱትን የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸውን ዕቃዎች ወይም ምርቶች እየገዛ ይጠቀማል። ገንዘብ በባንክም ሆነ በቀጥታ ለዴፓርትሜንት ሁለት ይተላለፋል። በዚህ መልክ በጠቅላላው ኢኮኖሚክ ውስጥ ልክ እንደ ደም ዝውውር የማያቋርጥ ግኑኝነትና መሽከርከር ይፈጠራል። ስለሆነም ይህ ሁኔታ አጠቃላይ የሀብት ክምችትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲፈጠር በማድረግ ለጠቅላላው ስርዓት ልዩ ዕምርታን ይሰጠዋል። ይህ ዐይነቱ የአመራረት ስልት ሲደራጅና ኢንዱስትሪዎች በዚህ መልክ ሲቀናጁ ስለ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የተስፋፋ የሀብት ክምችት ዘዴ(Expanded Accumulation) በመባል ይታወቃል። በዚህ ዐይነቱ ተከታታይነት ያለው የሀብት ማከማቻ ዘዴ ውድድር ከፍተኛ ቦታን ይይዛል።  ቀደም ብሎ እንደተተነተነው በካፒታሊስቶች መሀከል ባለው ፉክክርና የማምረቻን ዋጋ ቀንሶ ገበያ ላይ ለመቆየት ሲባል ካፒታሊስቶች በየጊዜው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲተክሉ ይገደዳሉ።

ገንዘብና የገንዘብ ሚና፣ እንዲሁም የገንዘብ ወደ ፊናንስ ካፒታል የመለወጥ  ሂደት !

ዛሬ የጥቂት አገሮች በተለይም፣ የአሜሪካን ዶላርና ኦይሮ ገንዘቦች ወይም ከረንሲዎች ዋናዎቹ የዓለም ንግድ መገበያያና የሬዘርብ ወይም የሀብት መከማቻ ዘዴዎች መሆናቸው የአብዛኛዎች የሶስተኛውን ዓለም አገር ገንዘቦች ትርጉም እንዳሳጣ የማይታበል ሀቅ ነው። በተለይም በአብዛኛው የዓለም ህዝብ ላይ ዶላር ህሊናዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ደካማ አገሮች ወደ ውስጥ የራሳቸውን ገንዘብ በተለያየ መሳሪያ በማንቀሳቀስ ለመዋዕለ-ነዋይ ተግባራዊ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የካፒታሊዝም ዕድገትና ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀት፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የጥቂት አገሮች ከረንሲዎች አይሎ መውጣት ተፈጥሮአዊና፣ ለጥቂት አገሮች የተሰጠ ችሮታ ተደርጎ በመወሰዱ  ነው። ይህንን የተዛባ ሁኔታና አመለካከት ለመረዳትና በመጠኑም ቢሆን መልክ ለማሲያዝ ገንዘብ በካፒታሊስት ህብረተሰብም ሆነ በሌሎች አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የተጓዘባቸውን ደረጃዎችና ዛሬ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ጠጋ ብሎ መመልከቱ  ጠቃሚ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው በገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ገንዘብ በተለያየ ዐይነት ብቅ ማለትና የንግድ መለዋወጫ መሳሪያ መሆን ከስራ-ክፍፍል መዳበር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በሌላ አነጋገር ከስራ-ክፍፍል መዳበርና፣ ገበያ የእህልና አንዳንድ የዕደ-ጥበብ ስራ ውጤቶች መለወዋጫ መድረክ ሆኖ ከመፈጠሩ በፊት ገንዘብ ቀደም ብሎ  አልተፈጠረም። አንዳንድ ማህበረሰቦች እንደኮሙኒቲ ሲሰባሰቡና የስራ-ክፍፍል ማዳበር ሲችሉና፣ በዚያውም አማካይነት ገበያ የሚለውን መድረክ ሲፈጥሩ፣ በተለያየ ኮሙኒቲና በግለሰቦች የሚመረተውን የተለያየ ምርት ለመለወጥ ወይም ለመሸጥ እንዲያስችል በመጀመሪያ አንድን ዕቃ ወይም ምርት በሌላ ተመሳሳይ ባልሆኑ ዕቃዎች ሲለውጡ፣ ይህ ዐይነቱ የልውውጥ ዘዴ አመቺ ሆኖ ስላላገኙት፣ ለሁሉም ገበያተኛ ተቀባይነት ያለው የሁሉም ዕቃዎች መለኪያ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚባል ነገር ፈጠሩ። በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ ዐይነቱ የመገበያያ መሳሪያ ራሱ የፍጆታ ባህርይ ሲኖረው፣ ለምሳሌ ፣ አሞሌ ጨው፣ ወይም ብረትና ልብስ እንዲሁም ሌሎች እቃዎች የገንዘብን ሚና በመጫወት እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ለገበያ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ  አድርገዋል።  ቀስ በቀስ አገዛዞች ሲቋቋሙና ስልጥናቸውን አስፋፍተው የተወሰነ ሀብት መቆጣጠር ሲጀምሩ፣ በጊዜው የተቋቋሙት መንግስታት ማህተም ያለበትና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊቀበለው የሚችል ገንዘብ አትመው የመገበያያ መሳሪያ ማድረግ ቻሉ። ይህ ዐይነቱ ማህተም ያለበት የገንዘብ ዐይነት(Coined Money) እንደየሁኔታው ከመዳብ፣ ከነሃስ፣ ከብርና ከወርቅ የሚሰራና፣ አማካይ ሆኖ የዕቃዎች መለዋወጫ ወይም የንግድ ልውውጥ መሳሪያ በመሆን የንግድ ፍጥነትንና የገበያ ኢኮኖሚ መዳበርን ማፋጠን ችሏል። ብዙ አገሮች ወደ ተወሳሰበ ስርዓት ከመሸጋገራቸው በፊት እንደዚህ ዐይነቱን፣ በመጀመሪያ ደረጃ የዕቃ በዕቃ ልውውጥ ላይ የተመሰረተ የገበያ ዕድገት በኋላ ደግሞ የንጉሶች ስዕል ያለበት፣ ከነሃስ፣ ከመዳብ፣ ከብርና ከወርቅ የተሰራ ገንዘብ ሲጠቀሙበት ነበር።

የገበያ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ እያደገ ሲመጣ ብርና ወርቅ በመፈራረቅ ዋናው የገንዘብ ዐይነት በመሆንና የንግድን ልውውጥ በማፋጠን ዐይነተኛ ሚና ተጫውተዋል። ይሁንና  ሁለቱም የገንዘብ ዐይነቶች የተፈጥሮ ውጤቶች በመሆናቸው እንደልብ የማይገኙ ስለነበር፣ በተለይም ወርቅ እንደልብ በማይገኝበት ጊዜ አንዳንድ መንግስታት የወርቅን ይዘት በመቀነስ የመግዛት ኃይሉ እንዲቀንስና የዋጋ ግሽበትም የታየበት ወቅት ነበር። በኢንዱስትሪ አብዮትና በማኑፋክቱር ማበብ የተነሳና የገበያውም መጠን እየሰፋ ሲመጣ ወርቅና ብር በማደግ ላይ ያለውን የንግድ ልውውጥ ሊያግዙና ሊያፋጥኑ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት በማደግ ላይ ያሉ እንደ እንግሊዝ የመሳሰሉ አገሮች ከረጅም ጊዜ ጥናት በኋላ በወርቅ የተደገፈ የወረቀት ገንዘብ ወደ ማተምና ዋናው የመገበያያና የምርት ክንዋኔ አጋዥ መሳሪያ ለማድርግ በቅተዋል። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ለመፈንዳት እስከተቃረበበት ጊዜ ድረስ የእንግሊዝ ፓውንድ ዋናው የመገበያያና የሀብት ክምች(Reserve Currency) መሳሪያ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ ልውውጥን ማፋጠን ችሏል። በሌላ ወገን ደግሞ እንግሊዝ በጊዜው የነበራትን የበላይነት ተጠቅማ ብዙ አገሮችን የነፃ ንግድ ፖሊሲን እንዲከተሉ በማድረግና በዚህ አማካይነትም የብዙ አገሮች የውስጥ ገበያ ማደግ ስላልቻለ፣ በተለይም ፈረንሳይና ጀርመን የመሳሰሉት ከእንግሊዝ ጋር የነበራቸውን የነፃ ንግድ ስምምነት በከፍተኛ ደረጃ በማቀዝቀዝና ወደ ውስጥ በማትኮር የእንግሊዝ የውጭ ንግድ ሚዛን ሊዛባ ችሏል። በተጨማሪም እንግሊዝ ብዙ ቅኝ ግዛቶች ስለነበሯትና እዚያ ያለውንም አስተዳደር መደጎም ስለነበረባት ከእንግሊዝ ወደ ሌሎች አገሮች የሚፈሰው ወርቅ እንግሊዝን እየጎዳት መጣ። በዚህም ምክንያት ፓውንድ እንደ ቀድሞው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ዋና የመገበያያና የሀብት ማከማቻ ዘዴ መሆኑ እያከተመ ይመጣል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በጦርነትና በኢኮኖሚ ብዙም ያልተጎዳችው አሜሪካ የእንግሊዝን ሚና ትወስዳለች። በ1944 ዓ.ም በብሬተንስ ውድስ ላይ በእንግሊዙ ታላቅ ኢኮኖሚስት ኬይነስና የአሜሪካኑ ተወካይ ኋይት መሀከል የጦፈ ክርክር ይደረጋል። በተለይም ኬይንስ የአሜሪካን ዶላር የዓለም አቀፍ የንግድ መለዋወጫና ሬዘርብ ከረንሲ እንዳይሆን አጥብቆ ቢከራከርምና፣ ከማንኛውም መንግስት ተፅዕኖ ውጭ የሆነ ባንኮር የሚባል አርቲፊሻል ከረንሲ ተግባራዊ እንዲሆን ቢሞክርም፣ ከአሜሪካኑ ተወካይ ከፍተኛ ቅዋሜ ስለደረሰበት ሳይወድ በግድ ዶላር ዋናው የንግድ መለዋወጫና የሪዘርብ ከረንሲ መሆኑን አምኖ ተቀበለ።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ አብዛኛው የኢንዱስትሪ አገሮች ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውን ሲገነቡና ቀስ በቀስም የውስጥ ገበያን ሲያስፋፋ፣ በዚያው መጠንም ወደ ውጭ የሚልኩት የኢንዱስትሪ ውጤት በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እየሆነ መጣ። በተለይም ምዕራብ ጀርመንና ጃፓን ወደ ውጭ የሚልኩት ዕቃ ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአሜሪካን ጋር በመወዳደር፣ የአሜሪካ የውጭ ንግድ እየተዳከመና፣ የአሜሪካን ዶላር ክምችትም በእነዚህ አገሮችና እንዲሁም በፈረንሳይ እየበዛ ሲመጣ፣ የአሜሪካን የወርቅ ክምችትም እየተናጋ ይመጣል። በብሬተንስ ውድስ ስምምነት፣ አሜሪካን ውጭ የተከማቸውን ዶላሯን በተለይም በከፍተኛ ደረጃ የንግድ ልውውጥ ከምታደርግባቸው አገሮችና በከረንሲ ከረጢት ውስጥ በተጠቃለሉ አገሮች ጋር ባደረገችው ስምምነት ዶላርን በወርቅ መተካት ነበረባት። በዚህም ምክንያት ከአሜሪካን ማዕከላዊ ባንክ ወርቅ ወደ ፈረንሳይና ጀርመን እየፈሰሰ በመምጣት ካዚናውን ማራቆት ይጀምራል። ስለሆነም በ1971 ዓ.ም አሜሪካን በራሷ ኃይል ስምምነቱን በማፍረስ ከእንግዲህ ወዲያ ዶላር በወርቅ እንደማይደገፍ ታስታውቃለች። በዚህም ምክንያት የተነሳ የዶላር ሚና ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይመጣል። ይሁንና አሁንም ቢሆን የአሜሪካ ኢኮኖሚ ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ ስለሆነና፣ አሜሪካንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የፖለቲካና የሚሊታሪ ተፅዕኖ በመጠቀም ዶላር የበላይነቱን ይዞ እንዲቆይ ለማድረግ ችላለች።  በተለይም የብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች ዕድገት ቆልፋ ለመያዝ  ኢኮኖሚው ከሚፈቅደው በላይ ዶላርን እያተመች በማስፋፋቷ በብዙ አገሮች ውስጥ ከየአገሩ የውስጥ ገንዘብ ይልቅ ዶላር የበለጠ ማምለኪያ ገንዘብ ሊሆን ችሏል ማለት ይቻላል።

ይህንን ትተን ወደ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ ስንመጣና፣ ገንዘብ በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ስንመለከት ከአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም የሆነበት ምክንያት አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ ኢኮኖሚዎች፣ የአሜሪካ፣ የጃፓን፣ አሁን ደግም የቻይና ኢኮኖሚ ወደ ውስጥ ሰፋ ባለ መልክ የተደራጀና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ስለሆነና፣ አብዛኛውም ህዝብ ተቀጥሮ የሚሰራ በመሆኑ፣ ገንዘብ  ከአንድ ኢኮኖሚ መስክ ወደ ሌላና እንዲሁም ወደ ባንክ፣ ደሞዝ ተቀባይ ከሆነው ደግሞ በንግድ አማካይነት፣ ከንግድ መስክ ወደ ኢንዱስትሪና ወደ ባንክ በፍጥነት በመሽከርከርከር ለገንዝብ ዕድገትና ባህርይ ልዩ መልክ ሰጥቶታል። በሌላ አነጋገር በውስጡ ገበያ መስፋፋትና፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል ባለው መተሳሰርና የንግድ ልውውጥ የተነሳ ከሶስተኛው ዓለም አገሮች ጋር ሲወዳደር የገንዘብ ሚና በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ልዩ ዐይነት አካሄድ ያለውና፣ በኢንዱስትሪና በተለያዩ መልኮች የሚገለጽ የሀበት ማከማቻ መሳሪያ ሊሆን ችሏል።  በቁጠባ መልክና በልዩ ልዩ ዘዴ ከህዝቡ የሚሟጠጠው ገንዘብ ወደ መዋዕለ-ነዋይነት ስለሚለወጥ በተለይም እንደ ዶላርና ኦይሮ፣ እንዲሁም የጃፓኑ ዬን በጣም ጠንካራ ገንዘብ ሊሆኑ በቅተዋል።

ወደ ሶስተኛው ዓለም አገሮች ስንመጣ ግን የውስጥ ገበያ ስነ-ስርዓት ባለው መልክ ሊስፋፋ ባለመቻሉ ከረንሲዎቻቸው በጣም ደካማ ናቸው። የኢትዮጵያና የተቀረው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ ከታች ወደ ላይ እያደገ የመጣ ባለመሆኑ፣ የገንዘብም ዕድገት እንደዚሁ ከታች ወደ ላይ ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር ተያይዞ ያደገ አይደለም። ስለሆነም ገንዘብ በመጀመሪያ ደረጃ እንደካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚዎች ቀስ በቀስ ከሌሎች ለፍጆታ ዕቃ ከሚውሉ ዕቃዎች ተላቆ በወርቅ አማካይነት በመገለጽና፣ የወረቀት ገንዘብም በወርቅ በመደገፍ ታትሞ ገበያ ላይ ሊቀርብ ባለመቻሉ፣ የገንዘብ ዕድገት የኢኮኖሚው ዕድገት ነፀብራቅ ለመሆን አልቻለም። ዝም ብሎ ከላይ ወደ ታች የተጫነ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከዚህም በላይ የአብዛኛው የአፍሪካ አገር ኢኮኖሚዎች፣ የአገራችንንም ጨምሮ በተሰበጣጠረና እርስ በርሱ ባልተያያዘ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ስለሚገለጽ ገንዘብ በፍጥነት ሊሽከረከር አይችልም። አብዛኛው ህዝብም ተቀጥሮ የማይሰራና፣ የሚሰራውም የሚያገኘው ገቢ በቂ ስላልሆነ፣ ገንዘብ በባንክ አማካይነት የሚተላለፍ አይደለም። የአብዛኛዎችም የንግድ ባንኮች ተግባር ኤክስፖርትና ኢምፖርትን ፋይናንስ ስለሚያደርጉና ለኢንዱስትሪ ተከላ መዋዕለ-ነዋይ ስለማያቀርቡ፣ ገንዘብ ማከናወን ያለበትን ተግባር እንዳያከናውን ተደርጓል። አብዛኛዎችም የአፍሪካ አገሮች ወደ ወጭ የሚልኩት ዕቃ የእርሻ ውጤትና የጥሬ-ሀብት በመሆኑ ከኢንዱስትሪ አገሮች ጋር በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። በሌላ አነጋገር አንድ የኢንዱስትሪ የምርት ውጤት ለማስገባት ብዙ ቶን ቡና ወይም ሌላ ያለተፈበረከ የጥሬ-ሀብት ማስተላለፍ ስለሚኖርባቸው ከውጭ ንግድ የሚያገኙት ገቢ የሚያመረቃና፣ ለውስጥ ገበያ መስፋፋት የሚያግዝ አይደለም። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በካፒታሊዝምና በተራ ገበያ መሀከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ችግር አለባቸው። ስለሆነም አገዛዞች ወደ ውስጥ ሰፋ ያለና፣ ህዝቦቻቸውን የሚያስተሳስርና፣ እንዲሁም ሰላምንና መረጋጋትን ሊያመጣ የሚችል ኢኮኖሚ እንዴት እንደሚገነባ ያልተገነዘቡ በመሆናቸው ያለውን ችግር የሚያባብስ በገበያ ኢኮኖሚ ስም የሚመጣ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገደዋል። ይህ ዐይነቱ ግራ መጋባትና መዘበራረቅ ለብዙ ዐመታት እንደሚቆይ መናገር ይቻላል። ከዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ችግር ለመውጣት የሚቻለው ቢያንስ ለሰላሳ ዐመት ያህል ወደ ውስጥ ያተኮረ በመንግስት የተደገፈ የአገር ውስጥ ግንባታ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ሲካሄድ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በየአገሩ ያለው የውስጥ ኃይል በመንግስት አስተባባሪነት በአንድነት መነሳት አለበት። የየአገሩም ምሁር ከራሱ ስሜትና ፍላጎት በመላቀቅ በቆራጥነት በአንድነት በአገር ስሜት በመነሳሳት ወደ ውስጥ ያተኮረ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚና የህብረተስብ ግንባታ ማካሄድ አለበት። ይህ ብቻ ሲሆን የየአገሩን ኢኮኖሚ በፀና መሰረት ላይ በመገንባት በሃማኖትና በጎሳ የሚናቆረውን ህዝብ መንፈስ በመሰብሰብ አትኩሮውን ወደ አገር ግንባታ እንዲያተኩር ማድረግ ይቻላል። በዚህም አማካይነት ቀስ በቀስ የአገር ውስጥ ገንዘብ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ሚና መረዳት ይቻላል።

     የመንግስት ሚና በካፒታሊዝም  የዕድገት ሂደት ውስጥ !

በአብዛኛዎቹ ለዩኒቨርሲቲ ተብለው በተዘጋጁ የኢኮኖሚ መጻህፍቶች ውስጥ፣ ለምሳሌ ስለ ማክሮና ስለ ሚክሮ ኢኮኖሚክስ የሚያትቱ መጽሀፍቶችን ለተመለከተ፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ካለምንም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በራሱ ኃይል እንዳደገና፣ እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሰና እንደሚንቀሳቀስ ተደርጎ ነው የተማርነው። የሚሰበከውምና የሚለፈፈውም ሁሉንም ገበያው ይቆጣጣረዋል፤ ያስተካክለዋል፤ ኢኮኖሚው ሲዛባ ራሱ ውስጥ ባለው ኃይል ሚዛናዊ እንዲሆን ያደርገዋል እየተባልን ነው የተማርነው። እንደሚነገረንና ለማሳመንም እንደሚሞከረው የመንግስት ጣልቃ ገብነት የገበያን ኢኮኖሚ ያዛባል፤ በተለይም በፊስካል ፓሊሲ የሚወሰድ ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ-ገብነት የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። መንግስት ከባንክ ወይም ከካፒታል ገበያ ላይ እየተበደረ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባቱ የግዴታ ከካፒታሊስቶች ጋር እንዲወዳደር ያደርገዋል። በካፒታሊስቶች ላይ ግፊት(Crowding out) ስለሚያደርግ ከገበያው እየተስፈናጠሩ እንዲወጡ ይገደዳሉ እየተባልን ነው ሲነገረን የከረመው።

ሀቁ ግን በኢኮኖሚ የግንባታ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ መልኮች መንግስት ጣልቃ ሳይገባ አጠቃላይ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የታየበት የምዕራብ አውሮፓ አገር የለም። በተለይም አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ከሰላሳ ዐመት ጦርነት በ1648 ዓ.ም ከተላቀቀቁ በኋላ ሆን ብለው የያዙት ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባት ነው። በጊዜው የከበርቴው መደብ ያደገ ስላልነበረና፣ የአብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚዎች በአማዛኙ በእርሻ ላይና በዕደ-ጥበብ ላይ የተመረኮዘ ስለነበር፣ ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለህብረ-ብሄር(Nation-State) ግንባታና፣ ህዝቡን ለማስተሳሰርና ብሄራዊ ስሜት እንዲኖረው ለማድረግ በፍጹም አያመችም ነበር። በመሆኑም የተገለጻለቸው ምሁራን የመንግስትንና እርስ በእርሱ የተሳሰረ ኢኮኖሚ ሚናን በመረዳት በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርጉ ነበር። ለዚህ ደግሞ፣ 1ኛ) የነቁ ኃይሎችን መደገፍ፣ 2ኛ) ወደ ውስጥ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መገንባት፣ 3ኛ) የውስጥ ገበያን ለመከላከልና በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች(Infant industries) ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት እንዳይጠቁ የታሪፍ ዕገዳ ፖሊሲ ማካሄድ፣ 4ኛ)ወደ ውጭ ደግሞ የተፈበረኩ ዕቃዎች በመላክ ወደ ውስጥ ወርቅ እንዲፈስ ማድረግ፣ 5ኛ) የዕደ-ጥበብ ስራዎችን ማስፋፋት፣ 6ኛ) መንገዶችንና ካናሎችን መስራት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የባቡር ሀዲድ በመዘርጋት ህዝቡ እንዲገናኝና እንዲተሳሰር በማድረግ  የንግድ ልውውጥ እንዲፋጠን ማመቻቸት፣ 7ኛ) ከተማዎችንና መንደሮችን ጥበባዊ በሆነ መልክ መስራት፣ ይህ በራሱ የአንድ ህዝብ መንፈስ የተረጋጋ የሚሆን ስለሚያደርግ የቤቶች አሰራር የተወሰነ የጂኦሜትሪ ቅርጽን ተከትለው እንዲሰሩ ማድረግ፤ እነዚህና ሌሎች ለአንድ አገር ግንባታ ይጠቅማሉ ተብለው የታሰቡ ነገሮች በሙሉ ተግባራዊ በመሆን ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት መጣል ችለዋል። በጊዜው የነበረውም ክርክር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንድን አገር ሁለንታዊ በሆነ መልክ ከማሳደግ ተነጥሎ መታየት እንደማይችልና፣ ህብረ-ብሄር፣ ህብረተሰብ፣ ባህል፣ ስነ-ምግባር፣ ሞራልና ሌሎች ህብረተሰብአዊ እሴቶች ተነጣጥለው ሊታዩ እንደማይችሉ በምሁራን የታመነበትና ትግል የሚካሄድበት ነበር። ስለሆነም መንግስት ብሄራዊ ኢኮኖሚ እንዲገነባ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድና፣ የህዝብም አለኝታ በመሆን ብሄራዊ ስሜት እንዲዳብር በተለያዩ መስኮች ላይ ድጋፍ በማድረግና እንደየሁኔታው ጣልቃ በመግባት ህብርተሰብአዊ ግንባታ እንዲፋጠንና መልክ እንዲይዝ ለማድረግ ችሏል። በምንም ምክንያት የየግለሰቦችን ተሳትፎ ሃሞት ለማፍሰስ የሚከተለው ተንኮላዊ ስራ አልነበረውም። በአጠቃላይ ሲታይ ራሳቸው ነገስታትም በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑና፣ አማካሪዎቻቸውም ፈላስፋዎችና የከተማ ገንቢዎችና ሳይንስቲስቶች ስለነበሩ አገርን ለመገንባት ይህን ያህልም ከባድ አልነበረም። በተለይም ደግሞ የትኛው ዐይነት የኢኮኖሚ ሳይንስና ፖሊስ ነው ለአገር ግንባታ ሊጠቅም የሚችለው በሚለው ላይ ሙሉ ስምምነት የነበረና፣ የተማረውም ለአገሩ ዕድገት ግንዛቤ ስለነበረው የአገሩን ጥቅም ለማስጠበቅና ህብረተሰብአዊ ስምምነት ለማምጣት ቀን ከሌሊት የሚሰራ ምሁራዊ ኃይል ነበር። በዚህም ምክንያት ጥበባዊ አገር ለመገንባት ከባድ አልነበረም።

ወደ አሜሪካ ስንመጣ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የነፃ ንግድ ፍልስፍናን በሚያራምዱና፣ ወደ ውስጥ ደግሞ በማኑፋክቱር ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ያስፈልጋል በሚሉ ኃይሎች መሀከል የጦፈ ትግል ይካሄድ ነበር። የመጀመሪያው የእንግሊዝን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ግን ብሄራዊ አጀንዳ የነበረውና አሜሪካንን ታላቅ አገር አድርጎ ለመገንባት የሚታገል ነበር። በመጨረሻ ላይ ብሄራዊ ስሜት ያለው የእነ ሃሚልተን ክንፍ በማሸነፍ የአሜሪካንን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመገንባት ቀስ በቀስ የበላይነት እንድትቀዳጅ መስመሩን ማስያዝ ቻለ።  ጃፓንና ደቡብ ኮሪያም፣ ከሞላ ጎደል ይህንን ዐይነቱን በመንግስት የተደገፈ ሁለንታዊ የኢኮኖሚ ግንባታ በመከተል ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ብሄራዊ ኢኮኖሚነት ለመሸጋገርና፣ ዛሬ ደግሞ በቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የቻሉት። ከሜጂ ዲይናስቲ በፊት የነበረው ቶኮጋዋ የሚባለው አገዛዝ የበለጠ በንግድ ላይ ያተኮረ ስለነበር፣ የሜጂ ዲይናስቲ ስልጣን ሲወስድ ቀስ በቀስ የቶኮጋዋን ደጋፊዎች በመግፋት የግዴታ ለውስጥ ገበያ የሚያመች የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ማካሄድ ይጀምራል። በተለይም ጃፓን በዚያው ዘመን በእንግሊዝና በተቀሩት ኃያል መንግስታት ተከባ ስለነበር የዚህን አደጋነት የተረዳው የሜጂ ዲይናስቲ የግዴታ አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰድ ነበረበት። በመጀመሪያ ወጣቶችን ወደ ውጭ ልኮ ማስተማር፣ ሁለተኛ የቴክኖሎጂ መማሪያ ኮሌጆች ማስፋፋት፣ በሶስተኛ ደረጃ፣ ለዕድገት አመቺ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ማጥናትና እሱን ተግባራዊ ማድረግ፣ በአራተኛ ደረጃ፣ ኢንስቲቱሽናል ሪፎርም ማድረግ ነበር። ለፈጣን ዕድገት ተስማሚ ርዕዮተ-ዓለም የነበረው ሱማራይ የሚባል በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሰለጠነ የሰው ኃይል በቆራጥነት በመነሳት ጃፓን ሁለት ትውልድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቴክኖሎጂ ባልቤት በመሆን ኢኮኖሚዋ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ካለፉት ሰላሳ ዐመት ጀምሮ ደግሞ ቻይና በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው የተወሳሰበና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየት የቻለችውና ወደ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የበቃችው ።

ከዚህ ስነነሳ የምንገነዘበው ለካፒታሊስት ኢኮኖሚ መሰረት የተጣለው በማኑፋክቱር አብዮት አማካይነት በፍጹም ሞናርኪዮች ነው። በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ገብነታቸውም ዕውቅና ለራሳቸው የግል ሀብት ለማካበት ሳይሆን፣ ንቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጣዊ-ኃይል እንዲያገኙ በክሬዲትና በኢንስቲቱሽናዊ የጥገና ለውጥ መስመር በማሲያዝና በመደገፍ ነው። በጊዜው የነበረው አመለካከትና ዕምነት ጠንካራ ህብረ-ብሄርን የመመስረቱ ጉዳይ እንደ ቅድመ-ሁኔታ በመታየቱና፣ በተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችም ዘንድ ፉክክር ስለነበር፣ ሁሉም በየፊናው የአገሩን ገበያና የአገሩን ከበርቴ ማጠናከር ነበረበት። ስለሆነም የአገር ውስጥ ገበያ እንዲዳብርና ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነባና ዕቃዎችና ካፒታል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በቀላሉ እንዲሽከረከሩ ለማድረግ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች ሁሉ ቀስ በቀስ መወገድ ነበረባቸው። የሰው አስተሳሰብ ከክላዊነት ወጥቶ ወደ ማዕከላዊነት እንዲያተኩር በማድረግ ኢኮኖሚው ህብረ-ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡም በተለያዩ ድሮች መተሳሰርና እንደ አንድ ህዝብ መነሳት አለበት የሚለው አመለካከት የታመነበት ጉዳይ ነበር። ካፒታሊዝምና ጠንካራ የውስጥ ገበያ ክልላዊ አስተሳሰቦች በሰፈኑበት አገር ውስጥ ማደግ አይችሉምና። ይህ በሞናርኪስቶች የተመራው የመርከንታሊዝም የኢኮኖሚ ግንባታ ነው የኋላ ኋላ ለእነ አዳም ስሚዙ የረቀቀው እጅ(Invisible Hand)  መንገድ የከፈተው። የእነስሚዝ  የነፃ ገበያ መሰበክ ከተጀመረም በኋላ የመንግስታት ጣልቃ ገብነት እየተወሳሰበና መልኩን እየቀየረ መጣ እንጂ፣ መንግስት ኢኮኖሚውን ለግለሰብ ተዋንያኖች ብቻ በመልቀቅ ምሽግ ውስጥ የገባበት ጊዜ አልነበረም።

በመሀከሉ የተወሰዱትን እርምጃዎች ሁሉ ትተን፣ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከተገባደደ በኋላ በመንግስታት የተወሰዱትን መልሶ የመገንባት እርምጃ ስንመለከት ኢኮኖሚው መንሰራራት የጀመረው እንደሚነገረን በገበያ ተዋንያን አማካይነት አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት የፈራረሱ ከተማዎቻቸውን መልሰው በመገንባት ለህዝቡ መጠለያ መስጠት ነበረባቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ የምግብን ችግር መቅረፍ ነበረባቸው። ቀጥሎም የንጹህ ውሃና የኃይል(Energy) ጉዳይ መፍታት ነበረባቸው። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነበር ኢኮኖሚውን መገንባት የሚቻለው። ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ የተረዱት የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት ስራ ለመስራት የሚችለውን ኃይል ሁሉ ማሰማራት ነበረባቸው። ለዚህ የሚሆን ደግሞ ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲስተም ማቋቋም ነበረባቸው። ስለሆነም ምዕራብ ጀርመን ብቻ ከ70-80% የሚጠጋው ከተማዎቿና ኢንዱስትሪዎቿ፣ እንዲሁም ድልድዮቿ የወደሙ ስለነበሩ  ከአስራአምስት እስከ ሃያ ዐመት ባለው ጊዜው ውስጥ ነው አገሯን መልሳ መገንባት የቻለችው። አገዛዞች የገበያ ተዋንያን መልሰው ይጠግኑታል ብለው እጃቸውን  አጣጥፈው አለተቀመጡም። ለዚህ ሁሉ ደግሞ ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ ከፍተኛ ዲሲፕሊን፣ ለስራ ታጥቆ መነሳት፣ የአገርን ክብር ለውጭ ኃይል ለመሸጥ አለመነሳት፣ የተከበረ አገር መገንባት የሚለው መመሪያ ነበር። በጊዜው የተለያዩ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ በሁሉም ዘንድ የነበረው ስምምነት ጠንካራ ኢኮኖሚና የተከበረች አገር መገንባት በሚለው ላይ ነው።

ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚውን መልሶ የመገንባት እርምጃ ቀጥተኛና ግልጽ ነበር። ኢኮኖሚው እያደገና ውስጠ-ኃይል እያገኘ ሲመጣ ደግሞ በሞኔተሪና በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት የእርማት እርምጃዎች መውሰድ ጀመሩ። እዚህ ላይ ነው ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገር ተማሪዎች የሚምታታበቸውና ስልጣን ላይ ቁጥጥ ሲሉ ብዙ ነገሮችን የሚያበላሹት። ያም ሆነ ይህ የመንግስት ሚና የተወሰነውን ሀብት ከመቆጣጠር አልፎ በፖሊሲ አማካይነት ጣልቃ እስከመግባት ድረስ ለካፒታሊዝም አጠቃላይ የሀብት ክምችት አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነበር። ለምሳሌ የምዕራብ ጀርመንን ኢኮኖሚ ስንመለከት፣ እስከ 90ዎቹ መግቢያ ድረስ፣ የአየር መንገድ(ሉፍታንሳ)፣ ፓስታ ቤት፣ የውሃ ክፍፍል፣ የመብራት ስርጭት፣ የባቡር ሃዲድ፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች፣ ስልክ… ወዘተ በመንግስት ቁጥጥር ስር ሆነው በአውቶነመስ ደረጃ በግሩም ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ነበሩ። አሁንም በአብዛኛዎቹ ላይ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዝ፣ ወደ ግላዊነት የተዘዋወሩት ደግሞ ከሃያ ዐመት ሙከራ በኋላ በተለይም በክፍለ-ሀገር ደረጃ ያሉት አስተዳዳሪዎች እንደገና መልሰው እየገዟቸው ነው። ምክንያቱም እንደ ንጹህ ውሃ ስርጭት፣ መብራትና ጋዝ የመሳሰሉት ካፒታሊስቶች ዋጋውን ስለሚያስወድዱና ትርፋማ ያልሆኑትን ስለሚዘጓቸው ይህ ጉዳይ አስቸጋሪ ሁኔታ ስለፈጠረና የህዝብንም ጩኸት ለመቀነስ ሲባል የግዴታ መልሶ መግዛቱ አስፈላጊነቱ ታየ። ከዚህም በላይ፣ በጀርመን አገር ብቻ ሶስት ዐይነት የባንክ አደረጃጀትና የአሰራርና ዘዴዎች አሉ። 1ኛ) በግል ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮች(Private Banks)፣ 2ኛ) በጋርዮሽ ስር ያሉ(Cooperative Banks)፣ 3ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ። ከዚህ በተረፈ ልዩ ዐይነት በዝቅተኛ ወለድ ብድር የሚሰጥ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ፣ ከሃምሳኛው ዓ.ም ጀምሮ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሲስተም አለ። በዚህ መልክ እነዚህ የተለያዩ ባንኮች የተለያየ ተግባር በመውሰድ ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮች ለትናንሽና ለማዕከለኛ አምራቾች ከረጂም ጊዜ አንፃር በዝቅተኛ ወለድ የሚከፈል ብድር ያበድራሉ። በጋርዮሽ ስር ያሉት ደግሞ ለአባሎቻቸው ብድር የሚያበድሩ ናቸው። ማንኛውም ማህበራዊ ነክ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በጋርዮሽ ባንክ አማካይነት ነው የሚንቀሳቀሱት።

ከላይ በአጭሩም ቢሆን የተዘረዘረው ጉዳይ የሚያሳየው ካፒታሊዝም በንጹህ መልክ በገበያ ኢኮኖሚ ህግ ብቻ የሚካሄድ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት አይደለም። የተወሳሰበና ብዙ ተዋንያን በህብረተሰብ ውስጥ ባላቸው ቦታ አማካይነት የሚካፈሉበትና፣ ሁሉም የተሻለ ድርሻ ለማግኘት ሲሉ በግልጽም ሆነ በይፋ ትግል የሚያደርጉበት መድረክ ነው። እዚህ ላይ ነው ብዙ የሶስተኛው ዓለም መንግስታት እስከዚህም የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ባህርይና እንቅስቃሴ በሚገባ ሳይረዱ በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖች እየተመከሩ የሚወስዱት ፖሊሲ ህዝቦቻቸው መቀመቅ ውስጥ ሲገቡ አንድ ቦታ ላይ ቆም ብለው ለመጠየቅ የማይችሉት።  ከላይ አንድ ቦታ ላይ እንደተተነው ካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ ክንውን ብቻ ሳይሆን ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ እንደመሆኑ መጠንና፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእያንዳንዱን የሰው ህይወት ሰለሚነካና ስለሚወስን የሚወሰዱት እርምጃዎች በሙሉ በዘፈቀደ አይደለም። በጉልበትና በአወቅኹኝ ባይነት በሚወሰዱበት ቦታ ደግሞ የግዴታ የሲቪክ ማህበራትን እንቅስቃሴና ጩኸት ያስከትላሉ። ስለሆነም እንደኛ አገር ዐይነቱ መንግስታት በየዋሁ ህዝባችን ላይ እንደሚጭነውና አገርን እንደሚያተራምሰው ዐይነት ፓሊሲ አይደለም በካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ፓሊሲ ተግባራዊ የሚሆነው። ከዚህ በመነሳት ነው የአገራችንን የኢኮኖሚ  ሁኔታና አደገ የተባለውን ኢኮኖሚ ማየትና ማንበብ ያለብን።

በአገራችን  የሚካሄደው ፖሊሲ፣ የኒዎ-ሊበራል፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ወይስ ሌላ  ዐይነት !

የድሮው የህውሃት አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ይደረግ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በግልጽ ለውይይት የቀረበ አይደለም።  እስከቅርብ ዐመታት ድረስ አገዛዙ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለብዙዎቻችን ግልጽ አልነበረም፤ አይደለምም። አገዛዙ ያካሂድ በነበረው የተምታታ ፖሊሲና፣ በተለይም ደግሞ „ስትራቴጂክ የሚባሉ መስኮችን“ ራሱ በመሰረተው ኩባንያና በአንዳንድ ከአገዛዙ ጋር በተቆላለፉ ሰዎች ቁጥጥር ስር በመዋላቸው ወደ ውስጥ ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚከተል ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ከመሞቱ በፊት ያናፈሰው „የዴቬሎፕሜንታል መንግስት” የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብዙዎቻችንን እንዳዘናጋና፣ በእርግጥም አገዛዙ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያካሂድ ይመስል አንዳንዶቻችንን ሲያጨቃጭቀን ሰንብቷል።  በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን መምሰል እንዳለበት ከአገዛዙ ጋር ክርክር ባለመደረጉ፣ እስካሁን ድረስ አገዛዙ ሰፊውን ህዝብ ለማዘናጋት ይሰብክ ይነበረው እሱ የሚያካሂደው ፖሊሲ አማራጭ የሌለውና፣ ይኸኛውም ብቻ „የዴቬሎፕሜንታል ስቴት“ መንገድ ሲሆን፣ ተቃዋሚው ደግሞ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊስን የሚናፍቅና እሱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገል ነው በማለት ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል። ይሁንና ግን ለአልተማረው ሰፊው ህዝብ ቀርቶ ለተማረው እንኳ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን እንደሚመስል ግልጽ አይደለም። ሰፋ ያለ ምሁራዊ ክርክር በማይደረግበት፣ የህዝብና የአገር ተቆርቋሪ በሌለበት አገር እንደወያኔ የመሳሰሉ ጮሌዎች ህዝብን ለማደናበር በቀላሉ ያመቻቸው ነበር።

ሀቁ ግን ወያኔ ስልጣን ከያዘ ከአንድ ዐመት በኋላ ከዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ተጽፎ የመጣለትን „የተቅዋም ማስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ“(Structural Adjustment Program) እየተባለ የሚታወቀውን፣ ከ1980 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ለአፍሪካ አገሮችና ለተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች የቀረበላቸውንና ተግባራዊ ያደረጉትን፣ በጠቅላይ መለሰ ዜናዊ የሚመራው አገዛዝ ተግባራዊ አድርጓል። የዚህም ፕሮግራም ዋናው ዓላማ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የገበያን ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ምድር ተግባራዊ አድርጎ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ ነው የሚል ነበር። ስለሆነም ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ለኢኮኖሚው አለመንቀሳቀስ እንቅፋት ናቸው ተብለው የተገመቱትን ማስወገድ ነበር። የፕሮግራሙ ዋና መሰረተ-ሃሳብ የመንግስትን በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ መግባት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ለኢኮኖሚ ተዋንያን(Invisible Hand) ገበያውን መልቀቅ ነው። በዚህም መሰረት፣ 1ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ፋብሪካዎችንና የንግድ ድርጅቶችን ወደ „ግል በወድድር ማዘዋወር ወይም መሸጥ፣“ 2ኛ) መንግስት ለማህበራዊ መስክ የሚያወጣውን ወጪ መቀነስ፣ 3ኛ) የውጭውን ኢኮኖሚ ሊበራላይዝ ወይም ልቅ ማድረግ፣ 4ኛ) ወደ ውስጥ በገበያ ላይ የሚደረገውን የዋጋ ቁጥጥር አንስቶ፣ የዕቃዎች ዋጋ በአቅራቢና በጠያቂ እንዲደነገግ ማድረግ፣ 5ኛ) የብርን የመግዛት አቅም ከአሜሪካን ዶላር ጋር በማነፃፀር ዝቅ (Devaluation) ማድረግ፣ ወዘተ… ናቸው። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ዕምነት መሰረት እነዚህ የተቅዋም ድክመቶች(structural weakness) ሲሆኑ፣ እነዚህ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሲደረጉ የገበያ ኢኮኖሚ በንጹህ መልኩ ተግባራዊ በመሆን፣ ሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ያገኛል፤ ገቢ ሲያገኝ በገበያ ላይ የሚሸጠውን ዕቃ ገዝቶ ይጠቀማል፤ የተወሰነውን በመቆጠብና ባንክ ውስጥ በማስቀመጥ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ለገበያው ኢኮኖሚ ዕምርታን በመስጠት ኢኮኖሚው እንዲያድግ ያደርጋል የሚል ቀላል የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ፎርሙላ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ የተቅዋም መስተካከል(Structural Adjustment) የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ጠጋ ብለን እንመልከት። እንደሚታወቀው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና፣ ይህንን ፖሊሲ የሚደግፈው ዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለው እንደዚህ ዐይነቱን ፕሮግራም በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ላይ ሲጭኑ መነሻቸው ሁሉም አገሮች ተመሳሳይ ችግሮች አሏቸው ከሚለው ቀላል ውሳኔ፣ ግን ደግሞ ሳይንሳዊ መሰረት ከሌለው ግምት በመነሳት ነው። እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ፖሊሲዎች እንደስትራክቸር ማየቱም ትክክል አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ፖሊሲዎች የአንድን ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ድክመት ማሳየት ቢችሉም፣ የስትራክቸራል ድክመቱ ዋና ምክንያት የጠቅላላው የኢኮኖሚ አወቃቀር ነው። ይህም ማለት የዳበረ የስራ ክፍፍል አለመኖሩ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኢኮኖሚው ስነስርዓት ባለው መልክ አለመደረጃቱ፣ ለዚህ ደግሞ እጅግ የተበላሸ ለኢኮኖሚ ዕድገት የማያመች የፖለቲካና የመንግስት አወቃቀር መኖሩ፣ በተጨማሪም የባህልና የህብረተሰብ ችግር አንድ ላይ ተደማምረው ኢኮኖሚው ውስጠ-ኃይል እንዳያገኝ ሊያደርጉት በቅተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አገራችንና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለሃምሳ ዓመታት ያህል የተከተሉት ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ የማያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ በዓለም አቀፍ የስራ-ክፍፍል ውስጥ በመካተት እንደ ቡናና ሌሎች ጥሬ-ሀብቶችን እንዲያመርቱ መደረጋቸውና፣ ለገበያ እንዲያቀርቡ መገደዳቸው ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀሩ ውስጠ-ኃይል እንዳይኖረው ለማድረግ በቅቷል። በዚህና በሌሎች በተሰበጣጠሩ አያሌ ምክንያቶች የተነሳ በተለያየ ጊዜያት ስልጣንን የጨበጡ አገዛዞች አንድ ወጥና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ኢኮኖሚ መገንባት አልቻሉም። ከዚህ ስንነሳ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ያቀረቡት የስትራክቸራል ሬፎርም ፕሮግራም የነበረውን ውስጣዊ ድክመት (Structural Weakness) የባሰውን ጥልቀት እንዲኖረውና እንዲጠናከር ያደረገ እንጂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል በተግባር ከተመነዘረ በኋላ ማረጋገጥ ችሏል።

እንደገና ወደ አጠቃላዩ ጽንሰ-ሃሳብ ስንመጣ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከማን ጋር አድጀሰት ወይም መስተካከል እንዳለበት ግልጽ አይደለም። በሌላ አነጋገር ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ፣ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ ወይስ ወደ ውጭ የዓለም ገበያንና ተዋንያኖችን ፍላጎት ለማሟላት በሚችል መልክ ማደራጀት ?  እንደገባኝና ፖሊሲውም በተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ማየት እንደቻልነው፣ ወደ ውስጥ ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያደኸይና በመንፈሱም ሆነ በአካሉ ደካማ ህዝብ ማፍራት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከላይ በተገለጹት ፖሊሲዎች አማካይነት ጥቂቱን አደልቦ በዓለም አቀፍ ሂራርኪ ውስጥ በማካተት አጠቃላይ የሆነ ዕድገት እንዳይኖር መንገዱን መዝጋት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የሆነ ማህበራዊ፣ ህብረተሰብአዊ፣ ባህላዊና የህሊና ቀውስ እንዲፈጠር አድርጎ ለብዙ ዐመታት ህብረተሰብአዊ መረጋጋት(Social Stability) እንዳይኖር ማድረግ ነው። ይህ ነው የኢኮኖሚ ፖሊሲው ዋና ዓላማ። በሌላ አነጋገር የኢኮኖሚው ፖሊሲ ሰፋ ያለ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተና ሊዳብር በሚችል ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ላይ ያተኮረ አይደለም።

ፖሊሲው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ለማረጋገጥ የተቻለው ድህነትን መቅረፍና ወደ አጠቃላይና ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ ግንባታ ማምራት ሳይሆን የባሰ ድህነትን መፈልፈልና የአገር ውስጥ ገበያ በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አገዛዙ የህዝብን ንብረት „ሲሸጥ“ ንብረቱ በቀጥታ በኢፈርት ስርና በአንዳንድ ከወያኔ ጋር የተቆራኙ እጅ ውስጥ ነው የወደቀው። ኢፈርትና አንዳንድ ግለሰቦች ገንዘብ ከንግድ ባንክ በርካሽ ወለድ በመበደር ፋብሪካዎችንና የንግድ ኩባንያዎችን በመግዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ማካበት ችለዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢፈርትና ከወያኔ ጋር በተሳሰሩ ግለሰቦች እጅ ወደ ስድሳ የሚጠጉ ፋብሪካዎችና የንግድ ኩባንያዎች ነበሩ። በዚህ አማካይነት አገዛዙና አንዳንድ ገለሰቦች የሞኖፖል ቦታ በመያዝ እጅግ ወደ ኋላ በቀረ ኢኮኖሚ ውስጥ ነፃ ውድድር እንዳይኖር ለማገድ በቅተዋል። ስለሆነም እንደተገመተው የተቅዋም መስተካከያ ፖሊሲው ነፃ ገበያን ሳይሆን ያመጣው የጥቂት ሰዎችንና የአንድ ኩባንያን ዘረፋንና መደለብን ነው።  በዚያው መጠንም ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ በብዙ መልኩ ሊገለጽ የሚችል የስራ-ክፍፍልና የውስጥ ገበያ(Home Market) እንዳይዳብሩ ነው ያገደው። ስለሆነም ለስራ ፈላጊው የስራ መስክ መክፈት አልተቻለም። በአንፃሩ ግን የውጭው ገበያ ልቅ በመሆኑ የሞባይል ስልክና የኢንተርኔት ሱቆች በመስፋፋት ከተማዎችን ማጠባብ ችለዋል። ወደ ገጠር ከተማዎች ሲኪድ ደግሞ ሳልቫጅና ከቻይና የመጡ ዕቃዎች በመፍሰስ ሰውን ባልባሌ ነገር ላይ እንዲሰማራ አድርገውታል። ይህ አጠቃላዩ ሁኔታ ደግሞ የባሰ ጥገኛና ለማኝ እንድንሆን አድርጎናል።

በእኛ ኢትዮጵያውን ምሁሮች በምንባለው ዘንድ የአገዛዙን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሚመለከት የተዛባ አመለካከት አለ። አንዳንዶች አገዛዙን እዚያው በዚያው እየተቃወሙ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በመንግስት የተደገፈ ፖሊሲ በአገራችን ምድር እንድሚካሄድ ይነግሩናል። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በመንግስት የሚደገፍ ፖሊሲ በመጀመሪያ ደረጃ ሁለ-ገብ መልክ ያለው ሲሆን፣ መሰረቱም ማኑፋክቱር ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው፣ በመንግስት የሚደገፍ የኢኮኖሚ ግንባታ የግለሰብ ተሳትፎን በፍጹም አይቃወምም። እንዲያውም የሚያበረታታና በዝቀተኛ ወለድ ብድር የሚያቀርብ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ በመንግስት የሚደገፍ ፖሊሲ በመጀመሪያ የሚወስደው እርምጃ መሰረታዊ ፍላጎቶችን(Basic Needs) ማሟላት ነው። ይህም ማለት፣ ለምግብ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የእህል አይነቶችን መትከልና በማስፋፋት በዚያውም መጠንም ሰፊው ህዝብ በምግብ ራሱን እንዲችል ማድረግ ነው። ከዚህ ቀጥሎ የንጹህ ውሃን ማቅረብ፣ ትምህርትቤቶችና የጤና መስኮች በየቦታው እንዲስፋፉ ማድረግ፣ ከዚህም በላይ ደግሞ ሰፊው ህዝብ ስነ-ስርዓት ያለው ኑሮ እንዲኖር በአገሪቱ ምድር ከአገራችን አየር ጋር የሚስማማና ዘላቂነት የሚኖራቸው ቤቶች እየሰሩ ለዝህቡ ማዳረስና፣ ህዝቡም በቤት ስራ ሊሰማራ የሚችልበትን ሁኔታ ማዘጋጀት መሰረታዊ የህዝብ ፍላጎቶች ናቸው።  የወያኔ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግን መሰረታዊ ፍላጎቶችን መሟላት ያልቻለ ነበር። በአራተኛ ደረጃ፣ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብሄራዊ ባህርይ ሲኖረው፣ ከውጭ የሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች የአገርን ኢንዱስትሪ እንዳያዳክሙ የእገዳ ፖሊሲ መከተል አለበት። ወያኔ ግን ይህንን አላደረገም። ባጭሩ የአገዛዙ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንግስት የተደገፈ(Developmental State Ecnomy) ሳይሆን፣ በጥቂት ሰዎች የሚዘረፍ ኢኮኖሚ ወይንም መንግስትን ተገን አድርጎ ዝርፊያ የሚያካሄድና(Predotary State)፣ አገራችን ከውስጥም ከውጭም እንድትጠቃ ያደረገና የሚያደርግ በዘረፋ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነበር።

በየቦታው የተተከሉትን የኢንዱስትሪ ዘርፎች ስንመለከት ደግሞ በመሰረቱ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥሩ የሚችሉ አይደሉም። የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ተብለው ታስበው የተተከሉና የሚተከሉ ሳይሆን ጥቂት ሰዎች ቶሎ ቶሎ ብለው በሀብት እንዲደልቡ የሚያመቹ የኢንዱስትሪ ተከላዎች ናቸው። አዲሱ የኢንዱስትሪ አተካከል ዘመቻ በ50ኛውን በ60ኛው ዓ.ም በብዙ የአፍሪካ አገሮችና በኛም አገር ይካሄድ የነበረውን ዐይነት በዚያው እንዲቀጥል ያደረገ የኢንዱስትሪ ተከላ ፖሊሲ ነው። እነዚህም እንደ መጠጥ የመሳሰሉ ፋብርካዎችን ማስፋፋት፣ ቀላል የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተከላዎች፣ የስኳር ተከላና ፋብሪካን ማስፋፋት… ወዘተ፣ የመሳሰሉት በመሰረቱ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ዕድገትን የሚቀናቀኑ የኢንዱስትሪ ተከላዎች ናቸው። እነዚህ አስፈላጊ ቢሆኑም  ተከታታይነት ላለውና ለፈጠራ የሚያመች የኢኮኖሚ ግንባታ የሚስማሙ አይደሉም። ከዚህም በላይ በተለይም በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተማዎች የተስፋፋው ብዙ ውሃንና ኃይልን የሚጋራና የሚጨርስ የሆቴል ቤቶች መስራትና ማስፋፋት ከአገራችን ስትራቴጂያዊ ፍላጎትና ከሰፊው ህዝብ ጥቅም ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም።

ባጭሩ የወያኔን የኢኮኖሚ ፖሊሲና የትራንፎርሜሽን ዕቅድ ከላይ በየቦታው በተዘረዘሩት መሰረተ-ሃሳቦች  መነፅርና በአንዳንድ አገሮች ውስጥ በልምድ ውጤትን ካስገኙ፣ በመንግስት በተደገፉ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ሚዛን ነው መመርመርና መለካት ያለብን። በመንግስት የተደገፉ የካፒታሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች  የሚያረጋግጡት፣ ፖሊሲዎቹ ብሄራዊ ባህርይ ሲኖራቸው፣ በመሰረቱ በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሎጂክ ላይ ያተኮሩ ቢሆኑም የመጨረሻ መጨረሻ ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ የሚከፍቱና ህብረተሰቡንም በብዙ ሺህ ድሮች የሚያስተሳስሩ ናቸው። በመሆኑም ጠንካራና የተከበረ አገር መገንባት ነው ዋና ዓላማቸው። ይህም ደግሞ በብዙ አገሮች በተግባር ተረጋግጧል። ከዚህ ስንነሳ ለብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያመቹ ቅድመ-ሁኔታዎች ቀስ በቀስ መዘርጋት ሊታለፉ የማይችሉ መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። ጤናማና ነፃ ውድድር፣ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ ከዚህም ባሻገር መሰረታዊ የሆኑ ለሀብት ክምችት የሚያገለግሉ ሁለት የኢንዱስትሪ መስኮች መኖር፣ እነዚህ ደግሞ በማሺን ኢንዱስትሪ መደገፍ ለአጠቃላይ የሀብት ክምችት ዋናው ቁልፍ እንደሆኑ በፖሊሲ አውጭዎችና በመንግስታቱ የታመነበት ጉዳይ ነው። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች በጭንቅላት ውስጥ ሲቋጠሩና እንደ ፖሊሲ መመሪያ ሆነው ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ሲሆኑ ብቻ ነው ሰፋ ያለ ህብረተሰብአዊና አገራዊ ሀብት መፍጠር የሚቻለው፤ ለሰፊው ህዝብም የስራ መስክ ሊፈጠር የሚችለው።  እንደሚታወቀው ሰፋ ያለ የስራ መስክ መክፈት የማይችል ኢኮኖሚ ደግሞ ውስጠ-ኃይሉ ውስን ብቻ ሳይሆን፣ የህዝቡም የመግዛት ኃይል ደካማ ስለሚሆን ኢንዱስትሪዎች ሊስፋፉና አዳዲሶችንም በመትከል ወደ አጠቃላይና ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መሸጋገር በፍጹም አይቻልም። የህዝቡ የመግዛት ኃይል በደከመበት ኢኮኖሚ ውስጥ ደግሞና፣ ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርሳቸው ባልተያያዙበት አገር ውስጥ ገንዘብ ከአንድ የኢኮኖሚ መስክ ወደ ሌላው በመሽከርከር ህብረተሰብአዊ ኃይል(Social Power) ሆኖ ሊወጣ አይችልም ማለት ነው። የአንድ አገር ገንዘብ መጠንከርና የመግዛት ኃይሉም ሊወሰን የሚችለው የውስጡ ኢኮኖሚ ከላይ በተዘረዘረው መልክ የተደራጀ እንደሆን ብቻ ነው። የተገላቢጦሽ ሊሆን በፍጹም አይችልም። የገንዘብን የዕድገት ታሪክ ለተከታተለ ከስራ-ክፍፍል መፈጠርና ማደግ፣ እንዲሁም መዳበር ቀደም ብሎ ገንዘብ አለተፈጠረም። ዕድገቱ፣ በፍጥነት መሽከርከሩና ጥንካሬው ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዘ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በገንዘብ ጥንካሬ ውስጥም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ የከተማዎች ማደግና መስፋፋት፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ የመገናኛና የመመላለሻ ዘዴዎች መገናኘት ለገንዘብ ጥንካሬና በፍጥነት መሽከርከር የራሳቸው ሚና አላቸው። እነዚህ ግን በገንዘብ አተማመን ስሌት ውስጥ ስለማይገቡ ስለአንድ ገንዘብ ጥንካሬ የሚኖራቸው ውስጣዊ አስተዋፅዖ ግልጽ ሆነው አይቀመጡም። ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ምንድ ነው? ዋናው ምክንያት ብዙ ነገሮች ተነጣጥለው ስለሚታዩ፣ አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ከሌላው ጋር ምንም ግኑኝነት ሳይኖረው ሊያድግ እንደሚችል ተደርጎ ስለሚወሰድ ነው። በዚህም ምክንያት በአንድ በኩል በገንዘብ መጠንከርና በኢንዱስትሪዎች ዕድገትና እርስ በርስ መተሳሰር፣ በሌላ ወገን ደግሞ በገንዘብ የመግዛት ኃይል ድክመትና በጠቅላላው ኢኮኖሚ አወቃቀር ድክመትና የውስጥ ገበያ አለመዳበር መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት መገንዘቡ ለወደፊቱ የአገር ግንባታ የተወሰነ ግንዛቤ ሊኖር ይችላል ብዬ እገምታለሁ።

ታዲያ  የኢትዮጵያ ን ኢኮኖሚ  ምን ዐይነት ስም  ልንሰጠው  እንችላለን ?

             ማንኛውም በሰው የማሰብ ኃይል የተሰራ ነገር ሁሉ ስምና ቅርጽ እንዲሁም ልዩ ዐይነት አገልግሎት አለው።  እንደዚሁም ማንኛውም አገር ወይንም ማህበረሰብ የሚመረኮዝበት ስርዓት አለው። ይህ ስርዓት በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በርዕዮተ-ዓለም የሚገለጽ ሲሆን የአንድን ህብረተሰብ የዕድገት ደረጃም ያሳያል። ከዚህ ውስጥ ለአንድ ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ ለመኖርና ለተከታታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የኢኮኖሚው አወቃቀር፣ የምርት ኃይሎች ሁኔታ ወይም የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የስራ-ክፍፍል መዳበር ወይም በአንድ አገር ውስጥ ከአንድ ነገር የተለያዩ ነገሮችን ማምረትና፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ ሙያ ተሰማርተው የተለያየ ምርት አምርተው በገበያ አማካይነት የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ ከሆነ የኢኮኖሚውን የዕድገት ደረጃና የሚንቀሳቀስበትን ህግና ስርዓት አንድ ስም ልንሰጠው እንችላለን። ስለሆነም አነሰም በዛም ማንኛውም ማህበረሰብ እንደ ዕድገት ሁኔታው የሚመረኮዝበትና የሚንቀሳቀስበት ስርዓት አለው። የአንድን አገር ኢኮኖሚ በስርዓት መግለጽ ጠቃሚነቱ የዕድገቱን ደረጃ ለመተንተን ብቻ ሳይሆን በህብረተሰብ ውስጥ የሚኖረውን የእርስበርስ ግኑኝነትና የገቢና እንዲሁም ገዝቶ የመጠቀም ኃይል ለማወቅ ነው። ስለሆነም የአንድን አገር ኢኮኖሚ ስርዓት ምንነትና ውስጣዊ ህግ ከታወቀ በአንድ የተወሰነ ወቅት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ ምክንያቱን በመፈለግ መፍትሄ ለመስጠት ያመቻል። ይህ ዐይነቱ ዘዴ በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ የተለመደና አጠቃላይም ሆነ በተወሰነ የኢኮኖሚ መስክ ንዑስ ክፍል ወስጥ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ በተቻለ መጠን መፍትሄ ለመፈለግ ከመንግስትም ሆነ በክልል ደረጃ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ምክንያቱም በአንድ አካባቢና መስክ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ በመስኩ የምርት ክንውን መቀዝቀዝ የተነሳ ከስራ መስኩ የመባረር ሁኔታ ከፍ ያለ ከሆነ ከስራው በሚባረረው ሰራተኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በዚያ አካባቢ በሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚም ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

ከዚህ ስንነሳ የእኛን አገር የኢኮኖሚ ስርዓት እንደዚህ ነው ብሎ ለመግለጽና የመንግስትንም ሚና ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ዘመናዊ የሚባል የኢኮኖሚ መስክ አለ። የዚህ መስክ የቴክኖሎጂ ደረጃ ዝቅ ከማለቱ የተነሳ በተለያዩ መስኮች ዘንድ መተሳሰር የለም። በሁለተኛ ደረጃ፣ በዚህ መስክ የሚመረተው አብዛኛው ምርት ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚያገለግል ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአብዛኛው ህዝብ ገቢ በጣም ዝቅ ከማለቱ የተነሳ ዘመናዊ ከሚባለው መስክ ውስጥ የሚመረተውንና ገበያ ላይ ወጥቶ የሚሸጠውን ምርት ገዝቶ ለመጠቀም አይችልም። ስለሆነም፣ በሶስተኛ ደረጃ፣ አብዛኛው ህዝብ የሚመካበት የኢኮኖሚ መስክ ኢንፎርማል መስክ በሚባለውና ከእጅ ወደ አፍ በሚመረት ምርት ላይ ነው። በአራተኛ ደረጃ፣ የመንግስትን በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና ስንመረመር በየጊዜው ተግባራዊ የሚሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ ከአገራችን ተጨባች ሁኔታ የሚነሱና የህዝቡን ችግር የሚፍቱ ሳይሆኑ እንዲያውም የባሰ ድህነትን የሚያስፋፉ ናቸው። ፖሊስዎቹ በሙሉ የጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከቱና የዓለም ኮሙኒቲውን ፍላጎት ለማሟላት እንጂ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ ገንብቶ ብሄራዊ ነፃነቷን ለማስጠበቅ አይደለም። ከዚህም ባሻገር የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ላይ እስከነበረበት ጊዜ ድረስ መንግስት በሚባለውና ራሱ ባደራጃቸው የኢኮኖሚ አውታሮች መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት ስለነበር ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለውድድርና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት እንቅፋት በመሆን ኢኮኖሚው ውስጣዊ ኃይል በማግኘት ከአንድ አካባቢ አልፎ በአገር ደረጃ እንዳይስፋፋ አግዶት ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ዘራፊ መንግስት የሚመስልና የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያጨናግፍ የህብረተሰብ ኃይል በመፍጠር ከውስጥ ወደ ወጭ በተለያየ መልክ ሀብት የሚፈስበትን ሁኔታ በማመቻቸት አገሪቱን ለማራቆት ችሏል። በአምስተኛ ደረጃ፣ የአገራችንን መሬት ለውጭ „ኢንቬስተሮች“ ለሚባሉት፣ በመሰረቱ ሀብት ዘራፊዎች በመሰጠቱ በአንዳንድ ቦታ የጌታና የሎሌ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነት በመፈጠር፣ በዚያው መጠንም የስራ-ክፍፍል እንዳይዳብርና የውስጥ ገበያ እንዳያድግ በራሱ በቂ ምክንያት ሊሆን ችሏል። በስድስተኛ ደረጃ፣ የአገሪቱ ገበያ ክፍት ከመሆኑ የተነሳ ይበልጥ እያደገ መምጣት የቻለው የአገልግሎት መስኩ ነው። ይህ ሁኔታ ገበያው ግልጽነት እንዳይኖረው ለማድረግ ችሏል። በሰባተኛ ደረጃ፣ ባንኮች ለኢንዱስትሪ ዕድገትና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚያደርጉት አስተዋፅዖ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ገንዘብ ወደ ካፒታል በመለወጥ አጠቃላይ የሀብት ክምችት እንዳፈጠር ተደርጓል። በስምንተኛ ደረጃ፣ መንግስት የሚባለውና ከመቶ ሚሊዮንን ህዝብ በላይ የሚያስተዳድረው አካል በራሱ ኃይልና ጥረት፣ እንዲሁም ፈጠራ ለአገሪታችን የሚስማማ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጣ ሳይሆን ከውጭ የሚመጣን ትዕዛዝ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ በተለይም በሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት ኢኮኖሚውን ማነቆ ውስጥ በመክተት ጠቅላላውንም ህዝብ በኑሮ ውድነት እንዲማረር ለማድረግ በቅቷል። በተለይም የኢትዮጵያን ብር በየወቅቱ ከዶላር ጋር ሲወዳደር የዋጋ ግሽበትን ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን የውጭውን ዕዳ ለመቆለልና የንግድ ሚዛኑም በከፍተኛ ደረጃ እንዲናጋ ተደርጓል።  ስለሆነም  ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሚኖርበት አገር ውስጥ የውስጥ ገበያው በደንብ ያላደገ፣ ከተማዎች በስርዓት ያልተገነቡበትና፣ በከተማዎች ውስጥም ሆነ በተለያዩ ከተማዎችና በክፍለ-ሀገራት ደረጃ ዘመናዊና ፈጣን የመመላለሻ ግኑኝነት ባለመኖሩ በብዙ ቦታዎች አብዛኛው ህዝብ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የሚኖር ነው የሚመስለው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተዘበራረቀ፣ ግልጽነት የሌለው፣ በሰለጠነ የስራ-ክፍፍል ያልዳበረና ውጥንቅጡ የወጣ የገበያ ኢኮኖሚ የሚመስል፣ ግን ደግሞ ወደ ካፒታሊዝም ሊሸጋገር የማይችል ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ግልጽነት የሌለውና የተዘበራረቀ የኢኮኖሚ ስርዓት ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት እንቅፋት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለዘረፋም የሚያምች ነው። በዚያው መጠንም አገራችን ለብዙ ዓመታት ከጥሬ-ሀብት አምራችነት ልትላቀቅ አትችልም ማለተ ነው።

ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ስንነሳ አማራጩ መንገድ በመንፈስ ተሃድሶ ላይ የተመሰረተ ሁለገብ የኢኮኖሚ ግንባታ ማካሄድ ብቻ ነው የሚያዋጣው። ለዚህ ደግሞ የመንግስቱ አወቃቀርና ሚና፣ እንዲሁም የቢሮክራሲው ሁኔታ መመርመር አለባቸው። በታሪክ ውስጥ እንደታየው መንግስታዊና ኢንስቲቱሽናዊ ሪፎርሞች ሳይደረጉ ጤናማና ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ በፍጹም መገንባት አይቻልም። ከዚህም በላይ ከኒዎ-ክላሲካልና ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተላቆ ግልጽ የሆነ ሰፊውን ህዝብ ወደ ስራ ሊያሰማራውና የአገርን ሀብት ለማንቀሳቀስ የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ማትኮሩ የማይታለፍ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም፣ በቀላሉ ተግባራዊ የሚሆኑና የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች ሊፈቱ በሚችሉ የቮኬሽናል ትምህርቶች ላይ መረባረብ እጅግ ጠቃሜ ነው። በመሆኑም፣ በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ ሊስፋፉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማዘጋጀት። ለዚህ ጥሩ ልምድ ካላቸው እንደ ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያና ጀርመን ጋር የጠበቀ ግኑኝነት መመስረት። በዚህ መሰረት ሁሉም ነገር ለአገር ግንባታ በሚለው ላይ በመረባረብ፣ በተለይም የውጭ ካፒታልን እንቅስቃሴ መቆጣጠርና፣ ወደ ውስጥ ደግሞ ባንኮች ለአገር ግንባታ ፋይናንስ እንዲያደርጉና፣ ይህም ከምርት ክንዋኔ ጋር እንዲያያዝ ማድረግ። በአገር ግንባታ ለመሳተፍ ለሚፈልገው ገንዘብ ላለው የአገር ውስጥ ከበርቴ ልዩ ስልጠና በመስጠት በትናንሽና በሚዲየም ሳይዝ ኢንዱስትሪዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ።  የመንግስት ዋናው ተግባር እነዚህን ሁሉ መልክ ማሲያዝ ሲሆን፣ በተለይም መሰረታዊ ነገሮች(Basic Needs) የሚሟሉበትን ሆኔታዎች ማዘጋጀትና መረባረብ። የአንድ መንግስትና የምሁሩ ታሪካዊ ኃላፊነት አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ዕውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው። ኢኮኖሚያዊ ድቀት በሰፈነበት፣ ሰፊው ህዝብ ካለምንም ኔትወርክ ተሰበጣጥሮ በሚኖርበት አገር፣ የኮሙኒቲ ኑሮ እንዳይመሰረት እንቅፋት በተዘረጋበት አገር፣ እዚህና እዚያ የፖለቲካ አክቲቪስቶች ነን ባዮች በሚቦርቁበት አገርና ወጣቱን በመቀስቀስ ህዝባዊ ዕልቂት እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት በሚደረግበት አገር ነፃና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አይቻልም። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አገር በክልል ተካሎ የየክልሉ አስተዳደሮች ራሳቸውን መንግስት ብለው በመጥራትና በካድሬዎቻቸው አማካይነት እዚያው ተወልዶ ያደገውንና በስራ ዓለም ላይ የሚገኘውን ህዝብ መጤ እያሉ በሚያሰቃዩበትና ቀዬውን ለቆ እንዲወጣ ጫና በሚደረግበት አገር ጤናማና ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አይቻልም።

ከዚህ ስንነሳ የአገራችን የወደፊቱን ዕድል ከሶስት መሰረተ-ሃሳቦች አኳያ መንደፍና መመልከት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይኸውም፣ 1ኛ) ጠንካራ-ህብረ ብሄር መመስረት፣ 2ኛ) አንድ ጠንካራ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ፣ 3ኛ) ለዚህ ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባት። እነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች በኢንፍራስትራክቸር፣ በከተማና በመንደር ግንባታዎች ተግባራዊነት የሚገለጹ መሆን አለባቸው። በእነዚህ አማካይነት ብቻ ነው አንድ አገር ከድህነትና ከልመና ልትላቀቅ የምትችለው። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው የሃሳብ ልውውጥ፣ ጥናትና ክርክር ማድረግ ያስፈልጋል። ሃሳቦች በሚዳፈኑበት አገር፣ ጥቂት ግለሰቦች የሃሳብ ሞኖፖል በያዙበት አገር ዕውነተኛና ፍቱን ዕቅድ መንደፍ አይቻልምና።

ከሁላችንም የሚጠበቀው መሰረተ-ሃሳብ !

ከሶስት ሺህ ዓመት ጀምሮ ለስልጣኔና ለነፃነት የተደረገውን ትግል ስንመለከትና ስንመረምር የፍልስፍና፣ የሳይንስና የቲዎሪ መሰረት የሌለው መንግስት አንድን ህዝብ የስልጣኔ ባለቤት ማድረግ እንደማይችል ነው። ይሁንና ግን አንድን ህዝብ የስልጣኔ ባለቤት ለማድረግ በሚደረገው ትግል ውስጥ ሁልጊዜ በሁለት መስመሮች መሀከል የጦፈ ትግል ይካሄዳል። ይኸውም ዕውነተኛ ስልጣኔና ስላምን በሚፈልገውና፣ ይህንን በሚጻረረው መሀከል የጦፈ ትግል መካሄዱ እንደ ተፈጥሮአዊ ህግ ሆኗል። በሌላ በኩል በቲራኖች ወይም ስልጣንን ላለመልቀቅ ያላቸውን ኃይል ተጠቅመው የህዝብን ትግል ለማፈንና ይህንን በሚቃወሙ መሀከል ያለው ትግል ግልጽ ነው። በታሪክ ውስጥ የሚያስቸግረው ትግል ቲራኖችን ወይም ጨፍጫፊዎችን ማጋለጡና መቋቋሙ አይደለም። ሁልጊዜ አስቸጋሪው ትግል በአንድ ጎራ የተሰለፉ ይመስል፣ ግን ደግሞ ዕውነተኛውን የስልጣኔ ፈለግ ለማሳሳትና፣ በዚህም በዚያም ብለው ስልጣን ላይ በመውጣት የአንድን ህዝብ የድህነት ዘመን በተዘዋዋሪ የሚያራዝሙትን ማወቁ ላይ ነው። በተለይም ምሁራዊና ሳይንሳዊ የውይይት ዘዴና ክርክር ባልተለመደበት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ሀቀኛውን የስልጣኔ አራማጅ፣ ሀቀኛ ካልሆነው ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሁለቱም አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ስለሚያስመስላቸው፣ የዋሆች ሀቀኛውን መንገድ ካሳሳቹ ለመለየት የሚቸገሩበት ጊዜ አለ። ስለሆነም ነው በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የህዝቦች ትግል የመጨረሻ መጨረሻ ሊወድምና ህዝቦች እንደገና ለሌላ የትግል ዙር እንዲዘጋጁ የሚደረገው። ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎች የነፃነት ትግል ከተካሄደባቸው የአፍሪካ አገሮች መማር የምንችላቸው ነገሮች አሉ። በተለይም በፐርሰናሊት ከልት አካባቢ ተገን የሚደረጉ ትግሎች አንድን ህዝብ በምንም ዐይነት ነፃ እንደማያወጡት ነው።

ስለሆነም ረጅም ጊዜ ቢፈጅም በሃሳብ ዙሪያ ከሚደረግ ትግል ውጭ ሌላ አማራጭ የትግል ዘዴ የለም። በተለይም አሁን ባለንበት በተወሳሰበ ዘመን፣ እንደ ዲሞክራሲ፣ መብትና ነፃነት የመሳሰሉት ጽንሰ-ሃሳቦች በዝርዝር መተንተን ያለባቸው መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። ከዚህ በመነሳት ነው ወደ ትልቁ የህብረተሰብ፣ የማህበረሰብ፣ የህብረ-ብሄር፣ የብሄራዊ ኢኮኖሚና የብሄራዊ ነፃነት ጉዳዮች ላይ መምጣት የምንችለው። በሌላ ወገን ግን የዲሞክራሲ፣ የመብትና የነፃነት ጥያቄዎች ከህብረተሰብና ከህብረ-ብሄር አስተሳሰቦች ውጭ ወጥተው ለብቻቸው ቢተነተኑና ትግል ቢደረግባቸው ትርጉም ሊኖራቸው አይችልም። ምክንያቱም ማንኛውም ግለሰብ መብቱንና ነፃነቱን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ብቻ ነው ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችለው። በሌላ አነጋገር፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄ ወደ ብሄረሰብ ደረጃ ዝቅ ብለው የሚታዩ ሳይሆን፣ ምንነታቸው ግልጽና ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው እንደ ህብረተሰብና እንደ ማሀበረሰብ በተደራጀ ህዝብ ውስጥ ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ አንድ ግለሰብም ሆነ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው እንዲያው ከአንድ አረመኔያዊ አገዛዝ በመላቀቁ ብቻ ሳይሆን፣ የመጨረሻ መጨረሻ ኑሮውን ለማሻሻል የግዴታ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ሲገነባለት ብቻ ነው።

በመሆኑም ትግላችን በብሄረሰብና በቡድን ዙሪያ የሚደረግ ሳይሆን፣ ህብረተሰብአዊና አገራዊ ባህርይ እንዲኖረው ያስፈልጋል።  በአንድ አካባቢ የሚደረግ እንቅስቃሴም ትርጉምነቱ ግልጽ ሊሆን የሚችለው ብሄራዊና ህብረተሰብአዊ ባህርይ ሲኖረው ብቻ ነው። በክልል ደረጃ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሳይንስና በፍልስፍና እንዲሁም በቲዎሪ በመደገፍ ከአጠቃላዩ የህብረተሰብ ጥያቄ ጋር መቀናጀትና መስመር መያዝ አለባቸው። ማንኛውም ታጋይ ነኝ እያለ ብሄረ-ሰቡንና ሃይማኖትን ተገን አድርጎ እዚህና እዚያ ቢንቀሳቀስም፣ ትግል ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት እስከሌለውና ከሌሎች  የህብረተሰብ ጥያቄዎች ጋር እስካልተቀናጀ ድረስ አንድ ብሄረሰብ የፈለገውን ያህል ቢንቀሳቀስም የመጨረሻ መጨረሻ ትግሉ በጥቂት ጮሌዎች ተነጥቆ የድህነተ ዘመኑ እንዲራዘም መደርጉ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ስለሆነም የአገራችንን ጉዳይ በሚመለከት፣ ከህብረተሰብ እስከ ማህበረሰብ፣ ከብሄራዊ ነፃነት እስከ ህብረ-ብሄርና እስከብሄራዊ ኢኮኖሚ ድረስ የምንከራከርባቸው አያሌ ነጥቦች አሉ። በተለይም ህዝባችን ከወያኔ አረመኔያዊ አገዛዝ ከተላቀቀ በኋላ በምን መልክ መደራጀት አለበት፣ ከመሰረታዊ ፍላጎቶች መሟላት አልፈን እንዴት አድርገን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ኢኮኖሚ መገንባት እንችላለን? በሚሉት መሰረተ-ሃሳቦች ላይ መወያየትና መከራከር አለብን። በእነዚህ ሃሳቦች ላይ ከሞላ ጎደል ግልጽነት እስከሌለ ድረስ ህዝባችን የሚመኘውን ዕውነተኛውን ነፃነት ሊጎናጸፍ በፍጹም አይችልም። ከዚህ ስንነሳ ወደ ውጭ ወጥተንና እየተገናኘን በአያሌ ነጥቦች ላይ መከረካርና መወያየት አለብን። ሀቀኛውን የትግል ዘዴና ውጤት አምጭውን ከአሳሳቹ ለይተን ለማወቅ ፊት ለፊት ተገናኝተን መከራከር አለብን።  ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ዕውነተኛ ብሄራዊ ነጻነትና ኢኮኖሚያዊ ድል ለመጎናጸፍ የሚቻለው ይኸኛውን ወይም ያኛውን ኃይል በመለማመጥ አይደለም። በተለይም በእኛ በኢትዮጵያኖች ዘንድ ፈረንጆችን መለማመጥ ትልቁ የትግል ስልት እየሆነ መጥቷል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን ባደረግን ቁጥር እየተናቅን እንደመጣን የገባን አይመስለኝም። ከዚህ ዐይነቱ „ዲፕሎማሲያዊ“ ከሚባለው አሳሳችና ድህነትን ከሚያራዝመው የትግል አካሄድ የግዴታ መላቀቅ አለብን። ደጋግሜ ለማሳየት እንደሞከርኩት ዓለም አንድ ኃይል ወይም ጥቂት ኃይሎች የባላይነትን ይዘው ለመቆየት የሚታገሉባት መድረክ ነች። አንደኛው አገር ወይም መንግስት ለሌላው አገር ነፃነትና ብልጽግና ጠበቃ ወይም አለኝታ ሊሆን አይችልም። በታሪክ ውስጥም ታይቶ አይታወቅም። አንድ ህዝብ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው በራሱ ጥረትና ኃይል ብቻ ነው።  ለዚህ ደግሞ በምሁሩ ዘንድ፣ በተለይም በግንባር ቀደምትነት እታገላለሁ በሚለው ዘንድ የሃሳብ ጥራት ያስፈልጋል። በተለይም ይህ ዐይነቱ ግንዛቤ ለአንድ አገር ብሄራዊ የኢኮኖሚ ግንባታ መሰረታዊ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ ዙሪያ ጠለቅ ያለ ሰፊ ውይይትና ክርክር ማድረግ ያስፈልጋል። በየትኛው የኢኮኖሚ ሳይንስ አማካይነት ነው ጠንካራ ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት የምንችለው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ የመመለሱ ጉዳይ እጅግ አስፈላጊ ነው።

fekadubekele@gmx.de