የህይወት ታሪክ
የዚህ ድረ-ገጽ ባለቤት የሆንኩት የመጀመሪያውን ከፍተኛ ትምህርቴን የተከታተልኩት ሲገንና ኤሰን በሚባሉ የጀርመን ከተማዎች ሲሆን፣ በርሊን በሚገኘው ፍሪ ዩኒቨርሲቲ(Free University of Berlin) ደግሞ በብሄራዊ-ኢኮኖሚክስ(National Economics) የማስትሬት ዲግሪዬንና፣ በዴቬሎፕሜንት ኢኮኖሚክስ(Development Economics) ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪዬን ለመቀዳጀት ችያለሁ። የዶክትሬት ዲግሪዬም ቴሲስ የኢትዮጵያን የማህብረሰብና የኢኮኖሚ ስርዓት የዳሰሰ ሲሆን፣ ለምን በኢትዮጵያ ምድር የገበያ ወይም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ለመዳበር አልቻለም? ምክንያቶቹስ ምንድን ናቸው? በሚል ለማተት የሞከረ የ480 ገጽ መጽሀፍ ነው። ትምህርቴን በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁኝ በኋላ በፍሪ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ በርሊን፣ በቢዘነስ ኮሌጅና በቴክኒካልና በኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ስለዴቤሎፕሜንት ኢኮኖሚክስ፣ ስለ ዓለም ንግድና፣ በሶስተኛው ዓለም አገሮችና በኢንዱስትሪ አገሮች መሀከል ስላለው የተዛባ የንግድ ግኑኝነት(Unequal Exchange)፣ ስለ ዓለም አቀፋዊ ዕዳና ተፅዕኖው(International Debt and its impacts on Third World countries)፣ ስለ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ሲስተም( International Currency System)፣ በተለይም የአሜሪካን ዶላር ለምን በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ መለዋወጫና የሀብት ማከማቻ ገንዘብ ለመሆን እንደበቃና፣ በተለይም የሶስተኛው ዓለም አገሮች በራሳቸው ገንዘብ ኢኮኖሚያቸውን እንዳይገነቡ እንቅፋት ለመሆን እንደበቃ አስተምሬያለሁ። በተጨማሪም የሁለቱን የብሬተን ውድስ ተቋማትን፣(Bretton Woods Institutions) ማለትም፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትንና(International Monetary Fund) የዓለም ባንክን (World Bank) አፀናነስና የርዕዮተ-ዓለም መሰረታቸውንና የአሰራር ቴክኒካቸውን በመመርመር እነዚህ ሁለት እህትማማች ተቋማት ለምን በሶሰተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና እርስ በእርሱ የተሳሰረ የውስጥ ገበያ(Home Market) ለማሳደግ እንዳልቻሉና እንደማይችሉም አስተምሬያለሁ። ከዚህም በሻገር በተለያዩ ኢንስቲቱሽኖች ውስጥ በመጋበዝ ስለ አፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ችግር ለማብራራት ሞክሬያለሁ፤ አሁንም እየተጋበዝኩ ገለጻ እሰጣለሁ። በተለይም የአፍሪካ ሀውስ(Africa House) በሚባለው ማዕከል ውስጥ በቋሚነት በራሴ ተነሳሽነት አንድ አገር በምን መልክ መገንባት አለበት? በሚል ከአውሮፓው የህብረ-ብሄር አገነባብ ስልት ልምድ በመቅሰም በፖለቲካና በመንግስት፣ እንዲሁም በፖለቲካና በአገር ወይም በህብረተሰብ ግንባታ መሀከል ያለውን ግኑኝነት ከሶስት ዐመታት በላይ ለማብራራት ሞክሬያለሁ። በተለይም የአንድ አገር ዕድገትና በአንድ አገር ውስጥ ሰላም መስፈን ሊወሰን የሚችለው በሰለጠነ የመንግስት መኪና አወቃቀርና በአንድ አገር ውስጥ በሚዘረጉ ልዩ ልዩ ተቋማት አማካይነት እንደሆነ ለማስተማርና ለማስረገጥ ሞክሬያለሁ፤ አሁንም በማስረዳት ላይ እገኛለሁ። ከዚህ በተረፈ አንዳንድ የአፍሪካ አምባሳደሮችን በማማከር በየአገሮች ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ችግር ለመገንዘብ ችያለሁ። በተለይም የፖለቲከኞችን በጣም ደካማ አስተሳሰብና የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ አወቃቀር የመረዳት ችግር እንዳለ ለመረዳት ችያለሁ። የዚህ ውጤት በየአገሩ የሚታየው የተዝረከረክ ሁኔታና የአገር ሀብትን አውዳሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል የስራ-አጥነትና የወንጀለኛ ቁጥር መብዛት ነው።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጀርመን አገር መጥቼ ትንሽ ወራት ከኖሩኩኝ በኋላ ያጋጠመኝና የመጀመሪያውን ንቃተ-ህሊና ማዳበር የቻልኩት ከማርክሲዝም ጋር ከተዋወቁኝ በኋላ ነው። በመጀመሪዎቹ ዐመታት የማርክሲዝምን ቲዎሪ የመረዳት ችግር ቢኖርብኝም ቀስ በቀስና ከጥልቅ ጥናትና ውይይት በኋላ መሰረተ-ሃሳቡን ለመረዳት ችያለሁ። በተለይም በጊዜው ያገኘኋቸው ከእኔ ቀደም ብለው የሄዱ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አሳሳች የሆነውን የስታሊንን የማርክሲዝም አተረጓገም እንዳልከተልና በዋነኛው ወይም በኦሪጂናሉ ላይ እንዳተኩር ስላበረታቱኝ በህይወት ባይኖሩም ሳለመሰግናቸው አላልፍም። ከዚህም በላይ የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ካላቸው የጀርመን ምሁራን ጋር የነበረኝና አሁንም ያለኝ የጠበቀ ግኑኝነት ለንቃተ-ህሊናዬ መዳበርና ለሊበራል አስተሳሰቤ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ የማይታበል ጉዳይ ነው። በዚህ ሳልወሰንና የማርክሲዝምን ቲዎሪ ገደብነትና የተግባራዊነቱን ችግር በመረዳት ሺለር ኢንስቲቱት ከሚባለው የዓለም አቀፍ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋር ለ20 ዐመታት ያህል አብሬ በመስራትና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ፣ በፍልስፍና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በማቲማቲክስና በልዩ ልዩ ለአገር ግንባታ በሚያገለግሉ ነግሮች ላይ ሰፋ ያለ ዕውቀት ለመሰብሰብ ችያለሁ። በዚህ ዐይነቱ ተቋማት ውስጥ ከአሜሪካንና ከልዩ ልዩ የአውሮፓ አገሮች የሚመጡ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የተቋሙ ቆርቋሪና ሃሳብ አፍላቂ ሊንደን ላሩሽ የሚባሉት ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው አሜሪካዊ ምሁር ነበሩ። ሚስተር ላሩሽ ከረጅም ጊዜ ምሁራዊ ትግል በኋላ በ96 ዐመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የዚህ ድህረ-ገጽ ባለቤት ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ይልቅ በእንደዚህ ዐይነቱ ተቋማት ውስጥ ገብቶ ሳይታክት መስራቱና በንቁ መሳተፉ ስለስልጣኔና ስለሰው ልጅ ዕድገት የበለጠ ግንዛቤ ሊሰጠው ችሏል ማለት ይቻላል። በዚህም መሰረት በአንድ አገር ውስጥ የሚደረግ ህብረተሰብአዊ ለውጥ በነጥብ በነጥብ ወይም በፕሮጀክት ደረጃ የሚካሄድ ሳይሆን ሁለ-ገብ መሆን ያለበትና፣ በተለይም በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ግንዛቤ እንደሚያስፈልግ ለመረዳት ችያለሁ። በተለይም የመንፈስ ተሃድሶ ሳይኖርና የተወሰነ የአሰራር ስልትን ሳያዳብሩና ዕምነትም ሳይቀዳጁ ለውጥ ማምጣት እንዳማይቻል ለመገንዘብ ችያለሁ። ባለፉት 25 ዐመታት በተከታታይ ለድህረ-ገጽ ያበረከትኳቸው ጽሁፎች የዚህ ዐይነቱ ምሁራዊ ተሳትፎ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ለዚህ ዐይነቱ ንቃተ-ህሊና መዳበርና ልዩ ልዩ ጽሁፎችን ለአንባብያን ለማበርከት የቻልኩት ባላቤቴና ልጆቼ ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ ስላደረጉልኝ ብቻ ነው። ካለነሱ አርቆ-አሳባኒትና ታጋሽነት እንደዚህ ዐይነቱን ስራ መስራትና በፖለቲካ ዓለም ውስጥም መሳተፍ ባልቻልኩ ነበር።
ከዚህ በተረፈ ጸሀፊው የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ህግና ዕድገት የሚያትት መጽሀፍ ጽፏል። ከባለቤቱም ጋር በመሆን 350 ገጽ የሚሆን የጀርመንኛ-አማርኛና፣ የአማርኛና የጀርመንኛ መዝገበ-ቃላት አሳትሞ ገበያ ላይ አቅርቧል። መዝገበ-ቃላቱ ተሻሽሎና አዳዲስ ቃላቶችን በማከል እንደገና ታትሞ ለገበያ ቀርቧል። በተጨማሪም „African Predicaments and the Method of Solving them Effectively“ በሚል አርዕስት ስር መጽሀፍ በመጻፍ ለአንባብያን አቅርቧል። መጽህፉን በተቹት መሰረት መጽሀፉ የአፍሪካን ችግሮችና መፍትሄዎቻቸውንም ቁልጭ ብሎ ያስቀመጠ ነው።
ይህንን ድረ-ገጽ ለማዘጋጀት ያነሳሳኝና ያበረታታኝ በየጊዜው ለንባብ የማቀርበውን ጽሁፍ የሚያነበው በአሜሪካን አገር ፊላዴልፊያ ከተማ ኗሪ የሆነው ውድ ኢትዮጵያዊ ጓደኛዬ አቶ ለይኩን ካሳሁን ነው። ስላበረታታኝና የሞራል ድጋፍ ስለሰጠኝ ሳላመሰግነው አላልፍም። ድህረ-ገጹን ለአዘጋጁት ኗሪነታቸው እዚሁ በርሊን ከተማ ለሆኑት ለወይዘሮ ኤለን ዊንድሙለርም(Ellen Windmüller) ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከዚህ በተረፈ አንድ የራሴ የሆነ ድህረ-ገጽ እንዳወጣ የወተወተኝና ከ25 ዐመት በላይ እንደ ወንድም በመሆን ያማከረኝንና ገንቢ ትችትና የሞራል ድጋፍ የሰጠኝን በጠባዩ እጅግ ግሩምና ቀና አመለካከት ያለውን ውድ ወንድሜን ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህን ሳላመሰግነው አላልፍም። በተጨማሪም እንደዚህ ዐይነቱን ድህረ-ገጽ እንዳዘጋጅ ላበረታታኝና ጽሁፌን በተከታታይ በማንበብ ገንቢ ሃሳቦች ለሚሰጠኝ ውድ ወንድሜን አቶ ጠና በጋሻውን ከልብ አመሰግነዋለህ።
ሚያዚያ 21፣ 2020
ፈቃዱ በቀለ