[gtranslate]

ፖለቲካም እንደ ሳይንስና እንደ ሂሳብ መታየት ያለበት ወይስ ሳይንሰ-አልባ !

                                                        ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                        ሚያዚያ 24፣ 2019

መግቢያ

ፖለቲካን በሚመለከት ከሂሳብ አንፃር ሳይሆን ከሳይንስ አንፃር ብቻ ለመጻፍ ሳወርድ ሳወጣ፣ አቶ ካሳሁን ነገዎ የኤስ ቢኤስ ጋዜጠኛና ቃለ-መጠይቅ ጠያቂ እ.አ በ03.04.2017 ዓ.ም በፖለቲካና በሂሳብ መሀከል ስላለው ግኑኝነት የሂሳብ አስተማሪና ተመራማሪ ለሆኑት ፕሮፌሰር ደጀኔ አለማየሁ ያቀረበላቸውን ጥያቄዎችና መልሶቹን ካዳመጥኩኝ በኋላ በዚህ አርዕስት ላይ ለመጻፍ ተገፋፋሁ። በመሰረቱ ለቀረቡት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች ካዳመጥኩኝ በኋላ በመልሱ በጣም መርካቴ ብቻ ሳይሆን፣ አገራችን ኢትዮጵያ እንደዚህ ዐይነት ምሁራንን ለማፍራት ችላለች ወይ ? ብዬ  ራሴን ትንሽ ለማጽናናት ሞከርኩኝ። በመሰረቱ ፕሮፌሰር ደጀኔ ፖለቲካ እንዴት ከሂሳብ ጋር ሊያያዝ ይችላል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄና ስለፖለቲካ ምንነት በደንብ ስላብራሩና አጥጋቢ መልስም ስለሰጡ ይህ ጽሁፌ የሳቸውን አተናተን የሚደግፍ ነው። ትንሽ የማክልበት ነገር ቢኖር ፖለቲካ የሚባለው ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት በአውሮፓ ምድር ውስጥ እንዴት አድርጎ ቀስ በቀስ ሊዳብር እንደቻለና ለዕድገትና ተቻችሎ ለመኖር የሚያስችል መሳሪያ በመሆን የተለያየ አመለካከት ባለቸው ፓርቲዎችና  የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተቀባይነትን እንዳገኘ ነው።

ፕሮፌሰሩ በደንብ እንዳብራሩት በአገራችንና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ስልጣንን የሚጨብጡ የገዢ መደቦች ፖለቲካ የሚባለውን ትልቅ ቦታ የሚይዘውን ጽንሰ-ሃሳብ ምንነቱን ስለማይረዱ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ዕውነተኛ ሀብትን የሚፈጥሩና የህዝቡን ኑሮ በማሻሻል የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር የሚያደርጉት አይደሉም። በሳቸው አባባል እንደኛ ባለው አገር ደግሞ ለስልጣን እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ስሜትን ስለሚያስቀድሙ ይህ ትልቅ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት መንደፊያና አገር ማስተዳደሪያ መሳሪያ መሰረተ ሃሳቡ እንዲዛነፍ ይደረጋል፤ እንዳየነው የብዙ ሚሊዮን ህዝብ ዕድልም ይበላሻል። ስለሆነም ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ ፖለቲካ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት መንደፊያ እንደመሆኑ መጠን የፖለቲካ ሰዎች ወደ አንዳች ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በሰፊውና በጥልቀት መመራመር አለባቸው፤ አሊያም በሳይንቲስቶችና በነገሩ ጥልቅ ዕውቀት ባላቸው ምሁራን መመከርና መረዳት አለባቸው ይላሉ። ይህ ሲሆን ብቻ አንድ አገር ወደ ተረጋጋና ወደ ዕድገት ሊያመራ ይችላል። እንደገና የአገራችን ሁኔታ ጠጋ ብለን ስንመለከት በአፄ ኃለስላሴ ዘመንም ሆነ በአብዮቱ ወቅት  የፖለቲካ ትርጉም በደንብ የተጠናና የተብራራ ባለመሆኑ በወቅቱ መሰራት የነበረባቸው የአገርን ዕድገት ሊያፋጥኑና የህዝባችንን ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ዕቅዶች በስራ ላይ ላይውሉ ቻሉ። እንደ ተከታተልነው በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን አገራችንና ህዝባችን ሁለ-ገብና ፈጣን ዕድገትን የማየት ዕድል ያገጣመቸው ሳይሆኑ ወደ ኋላ የሚጓዙ ነበሩ። ስለሆነም የአፄው አገዛዝ ፈጣን ዕድገትን ማምጣት ቀርቶ መሰረታዊ የህዝባችንን ችግር ሊፈታ የቻለ አልነበረም። የኋላ ኋላ እንደታየው አገራችን በረሃብ የምትጠቃና በልመና የምትታወቅ አገር ለመሆን በቃች። በአብዮቱ ወቅትም በጊዜው ቢያንስ በአዋጅ ደረጃ የታወጀውን የጥገና ለውጥ ተባብሮና ተቻችሎ አመራር በመስጠት ወደ ተግባር ከመመንዘር ይልቅ ስሜት በማየሉ የመጨረሻ መጨረሻ ለብዙ ሺህ ወጣትና ምሁራን ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ። በዚህ ወቅት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ደበዛው የጠፋበትና ሁሉም በስሜትና በደመ-ፍላት ግብ ግብ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነበር።

ወደ ዛሬው ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ ከዛሬ 26 ዐመት በፊት ስልጣንን የተቆናጠጠው ወያኔ የሚባለው ኃይል ቀደም ብለው ከተደረጉት ስህተቶች በመማር ሁሉንም ሊያሰባስብ የሚችል መድረክ በመፍጠር ስላም እንዲሰፍንና አገርን በአንድነት ለመገንባት ከመጣር ይልቅ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን በመከተል ተቻችሎና ተደማምጦ የመስራት ባህል እንዳይዳብር አደረገ። ዛሬ እንደምናየው ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ ፖለቲካ አገራችንና ህዝባችንን ትልቅ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚና የሞራል ቀውስ ውስጥ በመክተት ህዝባችን ግራ እንዲገባው አድርጓል። በዚህ መልክ አንዱ ከሌላው ስህተት ለመማር ባለመፈለግ በስሜትና በአቦሰጡኝ፣ ወይም በማንአለኝበት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ችግሩን ተደራራቢና ውስብስብ አድርገውታል። ይህ በእንደዚህ እንዳለ ዛሬ በግልጽ የሚታየውን ህብረተስብአዊና ኢኮኖሚያው ቀውስ፣ እንዲሁም የእሴት መከስከስን ከባህል ኋላ-ቀርነት አንፃር ለመመርመር የማይፈልጉ ኃይሎች የወያኔ አገዛዝ ቢወድቅ ችግሩ ከመቀጽበት የሚወገድ የሚመስላቸው ብዙ ኃይሎች በመፈጠር የፖለቲካውን መድረክ አጣበውታል። ስርዓት ያለው ጥናትና ጤናማ ውይይት እንዳይደረግ መንገዱን ሁሉ ዘግተውታል። በእነዚህ የጊዜው የፖለቲካ ተዋንያን ዕምነት በአገራችን ምድር ጎልቶ የሚታየው የተወሳሰበና በብዙ መልክ የሚገለጸው ችግር በቀላል ፎርሙላ ሊፈታ የሚችል ነው።

ከዚህ ስንነሳ በአለፈው አርባ ዐመት በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የተካሄደውን ትርምስ ስንመለከት ፕሮፌሰሩ በትክክል እንዳብራሩት አንድን አገር የማስተዳደሩ ጉዳይ በደንብ እንደ ሂሳብ ባለመጠናቱና ለአንድ የተወሳሰበ የሂሳብ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከፍተኛ ምርምርና ጭንቅት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ በፖለቲካውም መስክ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ግንዛቤ ውስጥ ባለመግባቱ ፖለቲካ የሚባለው ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ጽንሰ-ሃሳብ የማንም መተራመሻ በመሆን በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፣ እንዲሁም እናቶቻችንና አባቶቻችን ፍዳቸውን እንዲያዩ ተደርገዋል። ስለሆነም ፕሮፌሰሩ አጥብቀው እንዳሳሰቡት፣ ፖለቲካን የግዴታ ከሂሳብና ክፍልስፍና ጋር ማያያዙ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ኃላፊነትን የሚወስዱ ሰዎች የአንድን አገርና ህዝብ ዕድል የግዴታ ከተለያየ አንፃር መመልከት አለባቸው። ይህንን መሰረት በማድረግ ፖለቲካ ሳይንሳዊ ባህርይ እንዴት ለመያዝ እንደቻለ አጠር ባለመልክ ለመተንተን እሞክራለሁ።

ፖለቲካ  ማለት ምን ማለት ነው? ከሌሎች ነገሮችስ ተነጥሎ ሊታይ ይችላል ወይ ?

ፖለቲካ ሲባል አንድን አገር ጥበባዊ በሆነ መልክ ማስተዳደር ማለት ነው። እንደሚታወቀው ፖለቲካ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ እንደመሆኑ መጠን፣ ከሌሎች ነገሮች ተነጥሎ የሚታይና በግምት ወይም በስሜት ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን፣ ከፍተኛ የጭንቅላት ምርምርንና ከሌሎች ጋር መመካከርንና መከራከርን የሚጠይቅ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት የሚታቀድበት ሳይንስ ነው። ስለዚህም ፖለቲካ የአንድን ህብረተሰብ ሁለንታዊ ነገሮች፣ ማለትም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ህሊናዊ ነገሮችን የሚመለከትና የሚያጠቃልልም እንደመሆኑ መጠን ሳይንሳዊ ባህርይ አለው። ይህም ማለት፣ አንድ የፖለቲካ ፕሮጀክት ውሳኔ ከማግኘቱና ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት  በአጠቃላይ ሲታይ በህብረተሰብና በአገር ላይ፣ እንዲሁም በዛሬው ሁኔታና በወደፊቱ ትውልድ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖና፣ እንዲሁም አዎንታዊና አሉታዊ ውጤት በሚገባ ተተንትኖ መቅረብ አለበት። በመሆኑም ፖለቲካን ሳይንስ የሚያሰኘው ከአንድ አገር ነባራዊ ወይም የማቴሪያል ሁኔታዎች፣ የሰዎች የርስ በርስ ግኑኝነትና ህሊናዊ ሁኔታዎች ተነስቶ የሚነደፍ ፕሮጀክት በመሆኑ ሳይንሳዊ ያስብለዋል። ፖለቲካ የማይታይና የማይጨበጥ ቢሆንምና፣ እንደ ሌሎች የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ኢምፔሪካል በሆነ ዘዴ በላቦራቶሪ ውስጥ ሊረጋገጥ የሚችል ባይሆንም፣ በአንድ አገር ውስጥ በምድር ላይ የሚታዩትና በተለያየ መልክ የሚገለጹ ነገሮች ሁሉ የአንድ የፖለቲካ አካሄድ ነጸብራቆችና፣ የአንድ አገዛዝ መለኪያዎች እንደመሆናቸው መጠን ይህን ዐይነቱን ሁኔታ በፖለቲካ ሳይንስ መነጽር መገምገም ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የተዘበራረቀ ከሆነ፣ አንድ ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ከተገደደና ጥቂቶች ደግሞ ሀብትን የሚቆጣጠሩና የሚባልጉ ከሆነ፣ ስልጣናቸውንም መከት አድርገው ህዝብን የሚያሰቃዩ ከሆነ፣ በዚያው አገር ውስጥ ያለ የሰውና የተፈጥሮ ሀብት በመጣመር ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር አገዛዙ እንቅፋት የሚሆን ከሆነ፣ ታታሪ ሰዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር ዕድል የሚነፈጋቸው ከሆነና፣ አንድ አገር ጥበባዊ በሆነ መልክ እንዳይደራጅና ህዝቡም በአገር ግንባታ ውስጥ እንዳይሳተፍ  የሚከለከል ከሆነ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ፖለቲካ ከሳይንስ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፤ በፍጹም ፖለቲካም ሊባል አይገባውም።  በሌላ ወገን ደግሞ አንድ አገር ስርዓት ባለው መልክ የሚታቀድና የሚዋቀር ከሆነ፣ በአገር ውስጥ ያለን ሀብትና የሰውን ኃይል የሚያንቀሳቅሱ ልዩ ልዩ ኢንስቲቱሽኖች በየቦታው የሚቋቋሙ ከሆነና፣ የኢንስቲቱሽኖችም አስተዳዳሪዎች ኃላፊነታቸውን የሚረዱ ከሆነ፣ በአንድ የስራ መስክ ላይ ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች እዚህና እዚያ ተቋቁመው በመሀከላቸው የንግድ ልውውጥ የሚካሄድ ከሆነ ፣ በየቦታው ህዝብ ሊዝናናባቸው የሚችልባቸው ልዩ ልዩ መዝናኛዎች የሚቋቋሙ ከሆነ፣ መጽሀፍ ቤቶች፣ ሙዚየሞች፣ የቲአትር ቤት አዳራሾችና፣ ሌሎችም የወጣቱንና የህጻናትን ጭንቅላት የሚገነቡ ልዩ ልዩ መጫወቻዎችና ማሰልጠኛዎች በየቦታው ከተስፋፉ የሰፊው ህዝብ የማሰብ ኃይል መዳበሩ ብቻ ሳይሆን፣ ውስጠ-ኃይሉም ከፍ ያለ አዲስ ትውልድ ብቅ ሊል ይችላል። በዚህ መልክ የሚደራጅ ህብረተሰብ የሚሰራውን ስለሚያውቅ ፖለቲካውም አነሰም በዛም ሳይንሳዊ ባህርይ አለው ለማለት ያሰኛል።

በመሰረቱ የፖለቲካ ሳይንስ መሰረት ፍልስፍና ነው። በፍልስፍና ዓለም ውስጥ የተለያየ አመለካከት እንዳለ ቢታወቅም ፈላስፋዎች ሁሉ የሚስማሙበት አንድ ነገር ቢኖር የሞራል ወይም የግብረ-ገብን ጉዳይ ነው። የሞራል ጥያቄን በሚመለከት በተለይም በፖዘቲብ ወይም በሶፊስታዊ ሳይንስ የሰለጠኑ ምሁራን አመለካከት ሞራል በኢምፔሪካል ደረጃ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ሳይንሳዊ ሊሆን አይችልም፤ ከዚህም በመነሳት ፖለቲካ የሞራል ባህርይ ወይም ይዘት ሊኖረው አይችልም የሚል ነው። የፖዘቲቭ ሳይንስን መሰረት አድርገው የፖለቲካን ምንነት ለማስረዳትና ለመተንተን ለሚሞክሩ ምሁራን አንድ ነገር ሳይንሳዊ ሊሆን የሚችለው በሚታዩ ነገሮች(Facts) ላይ ሲመሰረትና ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በእነሱ ዕምነትም የህብረተሰብ ታሪክ፣ ባህላዊ ክንዋኔዎችና፣ በባህል አማካይነት የሚቀረጽ አስተሳሰብ ሳይንሳዊ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም።  ይህ ግን ስህተት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም አገር አነሰም በዛም የተለያዩ የህብረተሰብ የዕድገት ደረጃዎችን አልፏል። ስለሆነም እንደየሁኔታው ልምድን አካብቷል፤ ወይንም ደግሞ የባህሉ ሰለባ በመሆን አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠርና የተሻለ ዕድገትን ሊያይ አይችልም።  በሁለተኛ ደረጃ፣ የሰው ልጅ እዚያው በዚያው ሞራላዊና ስነ-ምግባራዊ የሚያሰኙት ነገሮች ራሱንና አካባቢውን ለመለወጥ የሚያስችለው የማሰብ ኃይል ስለአለው ነው። ከዚህ ስንነሳ አምላክ ከፈጠራቸውና የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውስጥ ካገኛቸው ተፈጥሮአዊ ነገሮች በስተቀር ማንኛውም በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮች፣ ማለትም ቤቶች፣ ጋርደኖች፣ ድልድዮች፣ የቴክኖሎጂዎች ዕድገት፣ ባቡርና አውሮፕላን፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ቁሳቁሳዊ ነገሮች በሙሉ የሰው ልጅ የጭንቅላት ውጤቶች ወይም በከፍተኛ ምርምር የተፈጠሩና የሰውን ልጅ ህይወት የሚያቃልሉ በመሆናቸው እዚያው በዚያው ሞራላዊ ናቸው። በሌላ ወገን ግን የሰው ልጅ በሙሉ ከሞራል ጋር የተፈጠረ ቢሆንም ሊያዳብረውና ሊያሳድገው የሚችለው የባህል ለውጥ ሲያደርግና ጥያቄዎችን በማቅረብ ለሚከስቱ ችግሮች ፍቱን መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ እንደሆነ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ከእንስሳ የተለየ እንደመሆኑ መጠን በአርቆ-የማሰብ ኃይሉ መመራት አለበት። ስለሆነም አንድ ህዝብ ታሪክ አለው የሚባለው ከእንስሳ ባህርዩ ሲላቀቅና በማሰብ ኃይሉ አማካይነት በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን በሙሉ መልክና ቅርጽ በመስጠት ለራሱ መጠቀሚያ ሲያደርጋቸውና ቀስ በቀስም ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ወደ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ማደግ ሲችልና ስርዓት ያለው ህብረተሰብ ሲገነባ ብቻ ነው። ስለሆነም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ዕድገትና ፀረ-ዕድገት መኖር ወይም መታየት ሊወሰን የሚችለው በየጊዜው በሚከሰተው የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ አማካይነትና፣ ባህላዊና ሞራላዊ ዕድገት ነው ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ ብቻ ነው ወደ ኢምፔሪካል ሳይንስ መምጣት የምንችለውና በቁጥር የምንለካው። በሌላ ወገን ግን ሁሉንም ነገር በቁጥር መለካት አንችልም። ሌላው የፖዘቲቭ ሳይንስን የምርምር ዘዴ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ ምሁራን ትልቁ ስህተት ሌሎች ፈላስፎችና ለየት ያለን የሳይንስ ፈለግ የሚከተሉ ምሁራን ተመሳሳይ ሁኔታን በሌላ መልክ ሊተረጉሙት እንደሚችሉ አይቀበሉም። ለምሳሌ እነሱ የካፒታሊስት ኢኮኖሚን የገበያ ኢኮኖሚና፣  በንጹህ መልክ ውድድር የሚካሄድበት ነው፣ ስለዚህም ሁሉም እንደ ፈለገው ገብቶ መወዳደር ይችላል ብለው ሲያስተምሩ፣ ሌሎች ለየት ያለ የአተናተን ዘዴና አመለካከት ያላቸው ምሁራን ደግሞ በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ግልጽ የሆነ የኃይል አሰላለፈና የምርት ግኑኝነት እንዳለ ያመለክታሉ። ስለሆነም ካፒታሊዝም በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል ባለ ግኑኝነት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ ግልጽ በሆነ የምርት ግኑኝነትና የመግዛት ኃይል ችሎታ የሚገለጽ ስርዓት በመሆኑ የአንድ ካፒታሊስት ዋና ዓላማው ምርትን የሚያመርተው የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን ትርፍ ለማግኘት ሲል ብቻ ነው ብለው ያብራራሉ። በተጨማሪም ካፒታሊዝምን ካፒታሊዝም የሚያሰኘው የገበያ ኢኮኖሚ በመሆኑ ሳይሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርት የሚመረትበትና በስራ-ክፍፍል መዳበር የሚገለጽ ስርዓት በመሆኑ ነው። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ደግሞ በፖዘቲቭ ሳይንስ የሰለጠኑ የዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖችና ተከታዮቻቸው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ ሳይመረምሩ ከቀረበላቸው ቁጥር ብቻ በመነሳት ኢኮኖሚው በዚህ መጠን አድጓል ብለው ከምድር ላይ ከሚታየው ሁኔታ ጋር ምንም የማይጣጣም ማብራሪያ ይሰጣሉ። በሌላ ወገን ደግሞ የድህነትን መስፋፋትና በከተማዎች ውስጥ የሚታየውን ምስቅልቅል ሁኔታ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ክስተትና፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚው ግኑኝነት ነፀብራቅ መሆኑን በፍጹም አይቀበሉም። ድህነትን፣ ምስቅልቅል ሁኔታንና የጥቂቶች በሀብት መባለግንና ህብረተሰብአቸውን ማመስ ጉዳያቸው ሳልሆነ እነዚህን ነገሮች እንደተፈጥሮአዊ እንጂ ሰው ሰራሽ አድርገው አይቀበሏቸውም። በመሆኑም ሌላ አስተሳሰብ ያለው አገዛዝና የምሁር ኃይል ችግሩን ከሳይንሳዊ አንፃር በመተንተን ፍቱን መፍትሄ ሊሰጥ ሲነሳ በሚችሉት መንገድ ሁሉ መሰናክል ይፈጥራሉ። ከዚህ አጭር ተነፃፃሪ አቀራረብ ስንነሳ የፖዘቲቭ ሳይንስ የምርምር ዘዴ አንድን ነገር ሁለንታዊ በሆነ መልክ እንድንተነትነው የሚረዳን አይደለም። በተጨማሪም ለአንድ ነገር መከሰት ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ሊጠቁመን ወይም ሊያስገነዝበን የሚችል ሳይንሳዊ መሳሪያ አይደለም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ሳይንስ መሰል ዕውቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመስፋፋቱና የምሁራንን ጭንቅላት በመያዙ ለመዝረክረክ፣ ለድህነትና ለሀብት መባከን፣ እንዲሁም ለጭቆና ዋናው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል።

ከዚህ ስንነሳ በታሪክ ውስጥ የተለያዩ ህብረተሰብአዊ አወቃቀሮችና ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ነበሩ ማለት ይቻላል። የፖለቲካን ምንነትና የህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት መንደፊያ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይንሳዊ ባህርይ የሰጡት የግሪክ ፈላስፋዎችና፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያለውና ስልጣንን የጨበጠው ሶሎን የሚባለው ታላቅ መሪ ነው። የግሪክ ፈላስፋዎች በጊዜው ፖለቲካን ከፍልስፍና ጋር ሲያጣምሩና ሳይንሳዊ ባህርይ ሲሰጡት፣ በመጀመሪያ ደረጃ በጊዜው ሰፍኖ ለነበረው የህብረተሰብ ቀውስና ርስ በርስ መተላለቅ ዋናውን ምክንያት በመረዳታቸው ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አንድ ህብረተሰብ የግዴታ ኃላፊነቱን በመረዳት ስርዓት ያለው ማህበረሰብ ሊገነባ የሚችለው በአዋቂዎች ሲመራና ራሱም ሲማር ብቻ መሆኑን በማመናቸው ነው። በእነሱም ዕምነት፣ ማንኛውም ህብረተሰብአዊ ቀውስና መዘበራረቅ ሊፈጠር የሚችለው ጭንቅላት በሚገባ ካልዳበረ ወይም ከተዘበራረቀ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር  አዕምሮው የተዘበራረቀበት የገዢ መደብም ሆነ ህብረተሰብ የሚሰሩትን ስለማያውቁ አገርን ከመገንባት ይልቅ ጦርነትና ዝርፊያን እንደባህል በመውሰድ አለመረጋጋትን ይፈጥራሉ፤ አዕምሮአቸውም የተጋረደ በመሆኑ ታሪክን የመስራት ኃይላቸው እየመነመነ በመሄድ የድህነትና የተስቦ በሽታ ሰለባ ይሆናሉ። ስለዚህም ይህንን ዐይነቱን የሰውን ልጅ ባህርይ የተረዱት የግሪክ ፈላስፋዎች ፖለቲካን ከፍልስፍና ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የዕውቀት ዘርፎች ጋር በማያያዝ  የአስተዳደር መመሪያ ያደርጋሉ። ስለሆነም በሶሎን ዘመን ተግባራዊ በሆነው ፖለቲካ አማካይነት የግሪክ ህዝብ የማሰብ ኃይሉ መዳበሩ ብቻ ሳይሆን፣ የፍልስፍና ምርምሮች፣ የማቲማቲክስና የሳይንስ ግኝቶች፣ የከተማ ዕቅድና የአርክቴክቸር ስራዎች እንደ አሸን በመፍለቅና ተግባራዊ በመሆን እስከዚያን ጊዜ ድረስ ህይወቱ ከጦርነትና ከመገበር ጋር የተያያዘው፣ በተለያዩ ደሴቶች ይኖር የነበረው የግሪክ ህዝብ ህይወቱ ይለወጣል፤ የማሰብ ኃይሉ በመዳበር ታሪክን በመስራት ከሌሎች ከፍልስፋናና ከሳይንስ ጋር ካልተዋወቁ አገሮች ወይም ጎሳዎች ጋር ራሱን በማወዳደር የተሻለና የሰለጠነ መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ ዐይነቱ ስልጣኔ በሮማውያን ወራሪዎች ከተደመሰሰ በኋላ የግሪክም ሆነ ገና የህብረ-ብሄርን አወቃቀርና አስተዳደርን የማያውቀው እዚህና እዚያ ተበታትኖ ይኖር የነበረው በጠቅላላው „የአውሮፓ ህዝብ“ እየተባለ ይጠራ የነበረው ወደ ፊት ሳይሆን የኋሊት ነበር የሚጓዛው። በአስረኛው ክፍለ-ዘመን የባላባቱ ስርዓት (Feudalism) በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቅ ሲልና ስር ሲሰድ አስተዳደሩ ግብታዊ እንጂ ሳይንሳዊ አልነበረም። ሬናሳንስ የሚባለው የግሪክ ስልጣኔ በአስራአምሰተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ እስከማለቱ ድረስ የአውሮፓ ህዝብ ዘራፊ በሚባሉና ስራቸው በሙሉ ጦርነት በሆነ የፊዩዳል አገዛዞች የሚተዳደርና ፍዳውን የሚያይ ነበር ማለት ይቻላል። የአውሮፓ ህዝብ ቀስ በቀስ በሬናሳንስ አማካይነት፣ በሬፍሮሜሽንና በኢንላይተንሜንት፣ (Enlightenment) እንዲሁም ደግሞ በተፈጥሮ ሳይንስ መዳበር ጭንቃላቱ ክፍት ሲሆንና ምሁራዊ ኃይልም እየዳበረ ሲመጣ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ዲስፖታዊ በመባል የሚታወቁ አገዛዞች ሳይወዱ በግድ ለሪፓብሊካን አስተሳሰብና ለግለሰብአዊ ነፃነት መንገዱን ክፍት ያደርጋሉ። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ሳይንሳዊ በመሆንና የግዴታ ከሞራልና ከፍልስፍና ጋር በመያያዝ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በተለይም በምሁር ደረጃ ተቀባይነትን በማግኘትና ምሁራዊ የመታገያ መሳሪያ በመሆን ቀሰ በቀስ ለፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ መንገዱን ማዘጋጀት ቻለ።

ይሁንና ግን በተለያየ ጊዜ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቅ ያሉት አገዛዞች እስኪሰለጥኑና  የሰውን ልጅ ባህርይ እስክይዙ ድረስ  የአውሮፓ ህዝብ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። የመቶ ዓመት፣ የስለሳ ዓመት፣ የሰባት ዓመት ጦርነቶችና ሌሎች ቁጥራቸው የማይታወቅ ትናንሽ ጦርነቶች እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተካሄዱና ለህብረተሰብ መፋለሶች መንገዱን ያመቻቹ ናቸው።  ያም ሆኖ ብዙ ጦርነቶች ተካሂደውና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ህይወታቸውን አጥተው እዚያው በዚያው ከተማዎች ይገነቡ ነበር፤ የዕደ-ጥበብ ስራዎችና ንግድ ይካሄዱ ነበር። የዚህ ዐይነቱ የስራ-ክፍፍል መዳበር የፊዩዳሉን ስርዓት ፈታ እንዲልና እንዲላላ እንዳደረገው ይታወቃል። በዚህም አማካይነት የተለያዩ የህብረተሰብ ኃይሎች በመፈጠርና በመፎካከር ፣ እንዲሁም ደግሞ ምሁራዊ ኃይሎች በመዳበር በፓለቲካ መድረኩ ላይ ግፊት ያደርጋሉ። በዚህም መሰረት በተለይም የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች በመዳበር በመጀመሪያ ደረጃ በመንግስት የተደገፈ ለህብረ-ብሄር ግንባታ የሚያገለግል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ይጀመራል። ይህ ዐይነቱ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይም ለግለሰብ ፈጠራ በሩን በመክፈት ከበርቴያዊ ኃይሎች እዚህና እዚያ ብቅ በማለት የፖለቲካ ማትሪክሱን ይለውጡታል። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ኃይል እያገኘ የመጣው የከበርቴው መደብ አገዛዞችን በዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመክተትና በማስገደድ የአገዛዝ የጥገና ለውጦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል። በአጭሩ የአውሮፓን ህብረተሰብ የፖለቲካ ዕድገት ስንመለከት ፖለቲካ እንደ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት መታየትና ግንዛቤ ውስጥ መግባት የተጀመረው ከምሁራዊ ዕድገት ጋር በመያያዝ ነው። በማንኛውም መልክ የሚገለጽ ዕውቀት ከአስራአምስተኛው ክፈለ-ዘመን ጀምሮ ሊፈጠርና ሊዳብር የቻለው በሌሎች አህጉሮች ሳይሆን በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቻ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው ግለሰቦች ቀሰ በቀስ ባቀጣጠሉት እሳት የተነሳና ሌላውም ይህንን ፈለግ ይዞ በመጓዝ እንዲስፋፋና እንዲዳብር በመደረጉ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በተገለጸላቸውና ተግተው በሚመራመሩና፣ አንድ ህዝብም በምን መልክ መደራጀት እንዳለበት በተገነዘቡ፣ የፍልስፍና፣ የህግ፣ የሃይማኖት፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የስዕልና የአርክቴክቸር ሰዎች፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የክላሲካል ሙዚቃ ደራሲዎችና አቀነባባሪዎች አማካይነት ነው የአውሮፓ የገዢ መደቦች ጭንቅላት ሊቀረጽና ህዝቡም በማወቅ ወደ ታሪካዊ ስራ  ማዘንበል የቻለው።  እስኪያዝን ጊዜ ድረስ ሰፍኖና የሰውን ጭንቅላት አፍኖ በመያዝ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ፀር የነበረው የካቶሊክ ጭፍን ሃይማኖትና የዘልማድ የአኗኗር ስራዎች ቀሰ በቀስ ሊወገዱ የቻሉት በፍልስፍና፣ በተፈጥሮ ሳይንስና የኋላ ኋላ ደግሞ በኢኮኖሚክስ ቲዎሪ መዳበር የተነሳ ነው። የህዋንና የተፈጥሮን ምንነት መረዳትና የሰውንም ልጅ የማሰብ ኃይል ተገንዝቦ ከተለያየ የፍልስፍና አቅጣጫ መተርጎምና መከራከር፣ እንዲሁም ከዚህ ክርክርና ምርምር ወደ ተግባር ሊመነዘር የሚችል ዕውቀት ማዳበር፣ ይህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ለውጥና ጭንቅላትን ማስጨነቅና በግልጽ የሚታይ ችግርን መፍትሄ ለመስጠት መሞከር  የአውሮፓው ባህል ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን መካድ ማለት የታሪክ ወንጀል እንደመስራት መቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ዛሬ የምንኖርበትን የቴክኖሎጂና የሳይንስ ዓለምን ለመረዳት አለመቻል ይሆናል።  ከየትም መጣ ከየት፣  ሳይንስ፣ ፍልስፍናና ማቲማቲክስ፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፈጠራና ዕድገት፣ በተጨማሪም ስርዓት ያላቸውና የታቀዱ ከተማዎችን መገንባትና ማስፋፋት የአውሮፓ ህዝብና የመንግስታቱ ባህል ነው ማለት ይቻላል። እንደዚህ ዐይነቱ የተመቻቸና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ አሰራርና የዕድገት ፈለግ በየጊዜው ለሚነሱ አገዛዞች በዚያው ላይ ተመርኩዘው ፖሊሲዎችን እንዲቀይሱና ፖለቲካን እንዲያካሂዱ ሊረዳቸው ቻለ።

ወደድንም ጠላንም፣ ተቀበልንም አልተቀበልንም የኢንዱስትሪ አብዮት መካሄድና የገበያ ኢኮኖሚ እየተባለ የሚታወቀውና በካፒታሊዝም ስርዓት የሚገለጸው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተው የምርት ክንዋኔና  የሀብት ማዳበሪያና ማከማቺያ ዘዴ የግዴታ ለፖለቲካ አስተሳሰብ መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል ማለት ይቻላል። በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ ዐይነቱ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የተያያዙ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው ኃይሎች በመፈጠር ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ጽንሰ-ሃሳብ የተለያየ ትርጉም በመስጠትና በዲሞክራሲያዊ መብቶች መስፋትና መጥበብ ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ በማድረግ ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ በጥንት ዘመን እነፕላቶንም ሆነ አርስቲቶለስ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ እነ ላይብኒዝ፣ ሺለር፣ ካንትና ሄገል ካዳበሩት የሞራልና የፍልስፍና ቲዎሪ እየተላቀቀ እንዲመጣ እንዳደረጉት መገንዘብ እንችላለን። በተለይም ካፒታሊዝም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በአሸናፊነት ሲወጣ ቀደም ብለው የነበሩ ሰብአዊ አስተሳሰቦችን ሌላ መልክ በማሲያዝ የዲሞክራሲ መብት ጥያቄም በምርጫና በህግ የበላይነት ብቻ የሚገለጽ ሆነ። ይህ ዐይነቱ የዲሞክራሲያዊ መብት አፈታት በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኃይል አሰላለፍ የሚያንፀባርቅና የራሱ የሆነ ውስንነት ያለው ነው። ስለሆነም ከዚህን ጊዜ ጀምሮም ለዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚደረገው ትግል ውስብስና አስቸጋሪ ይሆናል። በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በምዕራብ አውሮፓ ምድር ውስጥ በስራ ቦታ ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆናና መበዝበዝ፣ እንዲሁም ከሚፈለገው ሰዓት በላይ መስራት ወዝአደሩ የመብትን ጥያቄ እንዲያነሳ አስገደደው። የማርክስና የፍሪድሪሽ ኤንግስል ስራዎች መባዝትና መሰራጨት በአጠቃላይ ሲታይ በአውሮፓ ምድር ውስጥ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብን አመጣ። የወዝአደሩ እንቅስቃሴ ባየለበት እንደ ጀርመን በመሳሰሉ አገሮች ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ እንደነ ቢስማርክ የመሳሰሉት ባለስልጣናት የማህበራዊ ጥያቄን(The Social Question) ልዩ ግምት በመስጠት ሰራተኛው በዌልፈር አማካይነት መብቱ የሚጠበቅበት ሁኔታ ተዘጋጀለት። በተለይም ከእንግሊዙ ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አሉታዊ ውጤት ትምህርት የቀሰሙ የጀርመን ምሁራን የማህበራዊ ጥያቄን አጥብቀው በማንሳት በመንግስት ፖሊሲና ፖለቲካው ላይ ጫና ማድረግ ቻሉ። ይሁንና በጀርመን ምድር ውስጥ ሰፋ ያለ የፍልስፍናና የማህበራዊ ጥናት ቢካሄድም ይህ ዐይነቱ ጭንቅላትን የሚያዳብር ዕውቀት እያደገ በመጣው ከበርቴያዊ መደብ ጭንቅላት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሰርጎ ባለመግባቱና ዕውነተኛ የሪፓብሊካን አስተሳሰብ ባለመስፋፋቱ ከፊዩዳሉ ርዝራዥ የተረፈው የፕረሺያ ወታደርና ንጉሳዊ አገዛዝ የተቀዳጁትን ቴክኖሎጂ መሰረት በማድረግ ለመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ምክንያት ይሆናሉ። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሶቭየት ህብረትን ድምጥማጧን ለማጥፋት ስላልተቻለ አሜሪካና እንግሊዚ ሂትለርን በመደገፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሶቭየት ህብረት ላይ ጦርነትን እንዲያውጁ ያደርጋሉ። ይህ ማለት ምን ማለት ነው ? በአውሮፓ ምድር ውስጥ እንደዚያ ዐይነት ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ዳብሮና ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀት ታይቶ በጊዜው ስልጣንን የተቀዳጁ ኃይሎች የሰለጠነ ፖለቲካ ከማካሄድ ይልቅ ሌላ የሚቀናቀናቸው ኃይል እንዳይፈጠር ለማድረግ ጦርነትን በማወጅ ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሚሆኑ ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ስልጣንን የተቀዳጁት ኃይሎች የጠቅላላውን ህዝብ ደህንነት የሚጠብቁ ሳይሆኑ ከኢንዱስትሪና ከፊናንስ ካፒታል ጋር በመቆላለፍ ኢምፔሪያሊስታዊ ጦርነትን የሚያካሂዱና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርጉ ናቸው።  በሌላ አነጋገር፣ እስከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ የአውሮፓና የአሜሪካ ፖለቲካ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ለመምጣትና ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ ፕሮጀክትን ለመቀየስና ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማሳለፍ ነበረበት። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ግን አዲስ ሁኔታ በመፈጠር መንግስታት ኃይላቸውን በመሰብሰብ በአገር ግንባታ ሊረባረቡ ችለዋል።

ከዚህ ስንነሳ የምንገነዘበው ሀቅ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መኖርና ፖለቲካ እንደህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ግንዛቤ ውስጥ መግባት አስቸጋሪና የውጣ ውረድ ትግልን እንደሚጠይቅ ነው። ዛሬ እንደምናየው ራሱ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ የተጠናቀቀ እንዳይደለና፣ በእነዚህ አገሮች ያሉ ህዝቦች የሰለጠነ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካን ለመቀዳጀት የግዴታ የማያቋርጥ ትግል ማካሄድ እንዳለባቸው መገንዘብ ይቻላል። በምድር ላይ የሚታየውና በፖለቲካው ላይ ያለው ክስተት የሚጣጣሙ አይደሉም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ከተማዎች በስርዓት የተገነቡ ቢሆንም፣ ህዝቡም መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ቢሟሉለትና፣ የስራ ቦታም የማግኘት ዕድሉ ከፍ ያለ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣንን የሚቀዳጁ ፓርቲዎች ፖለቲካን በተለየ መልክ ስለሚተረጉሙት ውክልና ተሰጥቶናል በማለት ከየህገ-መንግስታቸው ጋር የማይጣጣም ፖለቲካ እንደሚያካሂዱ መገንዘብ ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ  በአንድ አገር ውስጥ ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መብት እንዲረጋገጥ ከተፈለገና አገዛዞችም የሰለጠነ ፖለቲካ ያካሄዱ ዘንድ የግዴታ ከህዝብ የፈለቁ በተለያዩ ዕውቀት የተካኑ ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ምሁራን መኖር አለባቸው። የእነዚህ ምሁራንም ተግባር አገዛዞች ፖሊሲ ሲያወጡና ፖለቲካ ሲያካሂዱ በጠቅላላው የህብረተሰብ አወቃቀርና ስነ-ልቦና ላይ ከአጭርም ሆነ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ክስተቶች በሚገባ የሚረዱና ለህዝብ የሚያስተምሩና የሚያስታዉቁ መሆን አለባቸው። ከዚህ ስንነሳ በአንድ አገር ውስጥ ፖለቲካ ሁለንተናዊነት ያለው ፅንሰ-ሃሳብ መሆኑን ግንዛቤ ማግኘት የሚቻለው በጠብንጃ ትግል የሚገኝ ሳይሆን ከማያቋርጥ የጭንቅላት ስራ ጋር የተያያዘ እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ የጭንቅላት ስራ አንድ ቦታ ላይ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል ሳይሆን የሚስፋፋና የሚዳብር፣ እንዲሁም ተከታታይነት ያለው መሆን አለበት። ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ለጥቂቶች ተለይቶ የሚሰጥ ወይም የሚተው ሳይሆን በየጊዜው መዳበር ያለበትና፣ የተለያየ ዕውቀት ያላቸውን ሁሉ የሚያካትት መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ቀስ በቀስ  ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ግንዛቤ ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ የመከራከር፣ በዕምነትና በፕሪንስፕል መስራትና፣ ከዚያም በላይ ሀቀኝነት በመዳበር፣ እዚያው በዚያው ደግሞ እየተፎካከሩ የመቻቻልና አብሮ የመስራት ባህርይ ማዳበር ይቻላል። በሌላ ወገን ደግሞ ምሁራዊ ታታሪነትና ታግቶ የመስራት ባህል ባልዳበረበት አገር ዲሞክራሲያዊ ባህልንና የሰለጠነ ፖለቲካን ማዳበር በፍጹም አይቻልም፤ ፖለቲካንንም እንደ ህብረተሰብአዊና እንደ ታሪካዊ ፕሮጀክት መረዳት አስቸጋሪ ይሆናል።  ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ትልቅ ጽንሰ-ሃሳብ በጥቂት ኃይሎች በመነጠቅና በቁጥጥር ስር በመዋል አንድን ህዝብ ማመሻና ሀብትን ማባከኛ በመሆን ታሪክ እንዳይሰራ ይደረጋል። ራሳቸው የመንግስትን መኪና የሚቀጣጠሩ ኃይሎች የድህነትና የጦርነት ዋናው ምክንያት ይሆናሉ ማለት ነው። መንግስትና ፖለቲካ ህብረተሰብአዊና ሳይንሳዊ ባህርይ ያላቸው ሳይሆኑ ማንም እንደፈለገው የሚዘባነንባቸው በመሆን ህዝብን ማስፈራሪያ ይሆናሉ። የማይነኩ፣  የማይከሰሱና የማይጠየቁ በመሆን የራሳቸውን ፍላጎት ያረኩበታል። ሰዎች መሆናቸውን በመዘንጋት አንድን ህዝብ ያሰቃያሉ። ታሪክ እንዳይሰራ መንገዱን ሁሉ ይዘጉበታል።

      በሶስተኛው ዓለምና በካፒታሊስት አገሮች መሀከል ያለው የፖለቲካ ግንዛቤ ልዩነት !

ዛሬ በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ የሰፈኑትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ሁኔታዎች ስንመለከት የእነዚህ አገሮች ሁሉ ችግር የማሰብ ኃይልን ማዳበር በሚችል ዘመናዊ(Modernization) እየተባለ በሚታወቀውና፣ የተለያየ ደረጃና ገጽታ ባለው ምሁራዊ ክንዋኔና ሂደት ውስጥ ማለፍ አለመቻላቸው ነው። ቀደም ብለው በተለያዩ ጽሁፎቼ ውስጥ ለማሳየት እንደሞከርኩትና፣ በዚህም ጽህፍ ውስጥ እንዳመለከትኩት ከግሪኩ ስልጣኔ ጋር ሲደመር የአውሮፓ ህብረተሰብ ቢያንስ አራት የዘመናዊነት ክንዋኔ ጋር ተለማምዷል ወይም በዚያው ውስጥ ለማለፍ ችሏል ማለት ችሏል። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የኢንዱስትሪ አብዮት ከመካሄዱ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ የተካሄደው የጭንቅላት ተሃድሶ ወይም የባህል ለውጥ ነው። በዚህ አማካይነት ነው ጭንቅላት ሲዳብርና በሁሉም አቅጣጫ ወደ ውስጥ መመልከት ሲጀምር የተወሰነው የአውሮፓው ህዝብ የሊትሬቸር ስራዎችን፣ ድራማን፣ ልዩ ልዩ ስም ያላቸውን የአርኪቴክቸር ስራዎችን ማዳበርና፣ ከዚያ በኋላ የዕደ-ጥበብን ስራ ያስፋፋል፤ በንግድ ልውውጥ አማካይነትም ይተሳሰራል። ይህ ዐይነቱ ከውጭና ከውስጥ የመጣ ህብረተሰብአዊ ለውጥና ከአንዳንድ አገሮች የተወሰኑ ሰዎች ሌላ ቦታ ሄደው በመጋባትና በመዋለድ ለአውሮፓው ህብረተሰብ ዕድገት እምርታን ይሰጡታል። እንደ አውሮፓ ህብረተሰብ በዘር የተቀላቀለና በመጋባት ልዩ ዐይነት ውስጠ-ኃይል የማግኘት ዕድል ያጋጠመው ሌላ ህብረተሰብ በፍጹም የለም። ወደ አሜሪካን ስንመጣም ተመሳሳይ ሁኔታ ማየት እንችላለን። ይህም የሚያረጋግጠው ማንኛውም አገር በራሱ ጥረት ብቻ ከሌሎች አገሮች ሃሳብን ሳይወስድና የባህል ልውውጥ ሳያደርግ በፍጹም አዳዲስ አስተሳሰቦችን ሊያፈልቅና ተከታታይነት ያለው ህብረተሰብ ወይም ማህብረሰብ ሊገነባ እንደማይችል ነው። ይህ ዐይነቱ የዕድገት ሁኔታ በሲስተም(System) ቲዎሪ የተደገፈና በተፈጥሮ ውስጥም የሚታይ ሁኔታ ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች በሙሉ ከተወሰኑት በስተቀር ካፒታሊዝም ከአደገና የበላይነትን(Monopoly) ቦታ ከያዘ በኋላ ነው ወደ „ህብረ-ብሄርነት“ የተሸጋገሩት። ይህም ማለት የካፒታሊዝም ወደ ተለያዩ አገሮች ለጥሬ-ሀብት ፍለጋ መስፋፋት ማርክስ እንደገመተው ካፒታሊዝም በእነዚህ አገሮችም ሊያድግና ሰፋ ያለ መሰረት ሊጥል አልቻለም። በአንፃሩ ግን ሁለንታዊ ዕድገትን የሚቀናቀን ሆነ። በጥሬ-ሀብት አምራች አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ሊስፋፋ አልተቻለም። በመሆኑም ካፒታሊዝም በቁንጽል መልክ በገባባቸው አገሮች ውስጥ ሁሉ የመንግስት አውቃቀሮች እንዲዛቡ በማድረጉ የዕድገት አጋዦች ሳይሆኑ አቆርቋዦች ለመሆን በቁ። አብዛኛው ዕውቀት የሚባለው ነገርም ከውጭ በቁንጽል መልክ የገባ በመሆኑና ከውስጥ በየአገሬው ምሁር እንዲፈተንና መከራከሪያ መድረክ ለመሆን ባለመቻሉ ይህ ዐይነቱ የተጣመመ የዘመናዊነት አካሄድ ጭንቅላትን ከማዳበር ይልቅ የበለጠ አድማስን በማጥበብ የዕድገት ተቀናቃኝ ለመሆን በቃ። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአንዳንድ አሜሪካን ኤሊቶች የተስፋፋው በኢምፔሪሲዝም ወይም በፖዘቲቭ ሳይንስ ላይ የተመሰረተው ዘመናዊ የሚባለው የዕድገት ፈለግና በጥቂት ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያተኩር የተደረገው፣ በተለይም የመንግስት መኪናዎችን በማደለብና አዲስ ቢሮክራሲያዊ ኃይል ብቅ እንዲል አመቺ ሁኔታን ሲፈጥር፣ በዚያው መጠንም የሴንተር-ፔሪፌሪ(Center-Periphery) ግኑኝነት እንዲፈጠር በማድረግ ወደ ውስጥ ህብረተሰበአዊ አውቃቀር እንዲዛባና እንዲዘበራረቅ አደረገ። ስለሆነም የመንግስትን መኪናና ፖለቲካውን የሚቆጣጠሩት የገዢ መደቦች የህዝቦቻቸው ተወካዮች ሳይሆኑ በቀጥታ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተጠሪና ታዛዥ በመሆን ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የታገዘና አጠቃላይ ወይም ደግሞ ሁለንታዊ የሆነ ዕድገት እንዳይመጣ አገዱ። ይህ ዐይነቱ የተዛባ የመንግስት አወቃቀርና ያልተገለጸላቸው አገዛዞችና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቶች የፖለቲካ መስኩን በመቆጣጠራቸው በየአገሮች ውስጥ የተገለጸለት የምሁር ኃይልና ሊወዳደር የሚችል ከበርቴያዊ መደብ ብቅ እንዳይል አደረገ። ይህ ሁኔታ በየአገሮቹ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ክፍተት እንዲፈጠር ለማድረግ በቃ።  ስለሆነም እጅግ የተዛባውና ከላይ የተወረወረው ዘመናዊ በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣው ባህል ዛሬ እንደምናየው በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለአምባገነን አገዛዞች መፈጠር ምክንያት ሆነ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲካ የሚባለው ህብረተሰብአዊና ህዝባዊ ፕሮጀክት ያለው ትልቅ ጽንሰ-ሃሳብ ወደ ግል-ሀብትነት በመለወጥ፣ እንዲሁም ደግሞ መንግስት የሚባለው መኪና የምዕራቡ የስለላ ድርጅቶች መሰግሰጊያ በመሆኑ ሀብትን ዘራፊ፣ አውዳሚና ወደ ውጭ በማውጣት የካፒታሊስት አገሮችን ዕድገት የሚያፋጥንና የሚያዳብር ለመሆን በቃ።  ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ብቅ ያሉትና የተዋቀሩት መንግስታትና አገዛዞች ካፒታሊዝም በአፍላው ዘመን የተጓዘበትን የመርካንትሊዝምን ፖሊሲ ተግባራዊ ሊያደርጉ አልቻሉም። ከዚህም በላይ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አብዛኛዎቹ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችና፣ እንዲሁም ደግሞ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ የዕድገት ፈለግና፣ የከተማዎችና የመንደሮች ግንባታ፣ እንዲሁም ደግሞ በሁሉም መልክ የሚገለጽ ባህላዊ ክንዋኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ፋታ ሲያገኙና ዕድል ሲሰጣቸው፣ በተለይም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ይህ ዐይነቱ ዕድል ተነፈጋቸው። አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ-አገዛዝ ነፃ ከወጡ በኋላ የራሳቸውን የዕድገት ፈለግ ሲቀይሱ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ይደረግባቸው ነበር። በዚህ መልክ ባለፉት 50 ዓመታት በውጭ ሰላዮች የተቀነባበረና የተደገፈ ከ60 በላይ የሚቆጠር የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተካሂዷል። መንግስታትና ብዙ የአፍሪካ አገሮችም የመረጋጋት ዕድል ሊያገኙና ያላቸውንም ሀብትና የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ በአገር ግንባታ ላይ እንዳይረባረቡ ታገዱ።

በተለይም „የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ“ በሚባለውና የዓለምን ማህበረሰብ በሚያተራምሰው ብዙ የአፍርካ አገሮች የገበያ ኢኮኖሚን ማካሄድ አለባችሁ እየተባሉና እየተገደዱ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክሎጂ ላይ የተመሰረተና፣ እንዲሁም እርስ በርሱ የተሳሰረ ሰፋ ያለ የገበያ ኢኮኖሚ እንዳያዳብሩና እንዳያስፋፉ አገዳቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳና፣ በየጊዜው በሚከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ በመወጠራቸው ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት ለመወጣት ሲሉ የግዴታ ከዓለም የካፒታል ገበያ ላይ ወይም ደግሞ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ ወይም ከካፒታሊስት መንግስታት ገንዘብ በመበደር የባሰውኑ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ይገደዳሉ። ለመክፈል በማይችሉበት ጊዜ ደግሞ እንደገና ብድር ለማግኝት ሲሉ „ከዓለም ኮሙኒቲው“ ተዘጋጅቶ የሚመጣ የአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Austerity Policy) ተግባራዊ በማድረግ የባሰውኑ ኢኮኖሚውን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በመክተት ባህላዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት ስለሌላቸውና በቀረጥ አማካይነት ከሰራተኛውና ከአሰሪዎች ገንዘብ በማግኘት ህብረተሰቡን ሊጠቅምና የህዝቡን አስተሳሰብ ሊሰበሰብ የሚችል ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የኢንፍራስትራክቸር ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ ስለማይችሉ ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ በመሸጋገር ሁኔታውን የባሰ ውስብስብ ያደርጋሉ። የብዙ አፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚዎችም በአንድ ወይም በሁለት ወደ ውጭ በሚላኩ የጥሬ-ሀብቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑና፣ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ(Rent Seeking) የጥሬ-ሀብት ማውጫዎችንና የእርሻ መሬቶችን ለውጭ ዘራፊ ኩባንያዎች ስለሚያከራዩ የባሰውኑ ኢኮኖሚውን በማዘበራረቅ የህብረተሰቦቻቸውን የማሰብ ኃይል ይረብሻሉ፤ ተግባራቸው ሁሉ ወዳልባሌ ቦታ ላይ እንዲውል ያደርጋሉ። አብዛኛዎቹ መንግስታት ካለማወቅ የተነሳ በሚያካሂዱት በሳይንስ ያልተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ እሴታዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመቶች በመከሰት የፓለቲካ መስኩን ያዘበራርቁታል።  ፖለቲካ የሚባለውም ከፍተኛ ትርጉም ያለው ጽንሰ-ሃሳብ በመጥፎ አስተሳሰብ በመመረዝ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ መፍጠሪያ እንጂ ያሉትን ችግሮች መፍቺያ መሳሪያ ሊሆን አልቻለም። በተለይም ግሎባላይዜሽን የሚባለው ፈሊጥ ከተስፋፋ በኋላ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታት የባሰውኑ በካፒታሊስት አገሮች ላይ ጥገኛ በመሆንና፣ የመንግስት መኪናዎቻቸውን የበለጠ ጨቋኝ በማድረግና በስለላ ድርጅቶች በመታጠቅ በመንግስታትና በህዝብ መሀከል ያለው ግኑኝነት በሁለት ጠላቶች መሀከል ያለ ግኑኝነት አስመስሎታል። በተለይም መንግስታት ሽብርተኝነትን መዋጋት አለባቸው ተብለው ስለሚወተወቱ አትኩራቸው ሁሉ አገርን መገንባት ሳይሆን ይህንን ዐይነቱን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በተባባሪዎቹ የሚመረተውን የሽብርተኛ ኃይል ለመዋጋት ሲሉ ያላቸውን ኃይል እዚያ ላይ እንዲያባክኑ ይገደዳሉ።

ይህንን መሰረት በማድረግ ነው በሌሎች የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ያለውንና ተግባራዊ እየሆነ የመጣውን ፖለቲካ የሚባለውን ጽንሰ-ሃሳብ መረዳት የምንችለው። አንዳንድ የአገራችን ምሁራን፣ በተለይም በውጭ ዓለም የሚኖረውና፣ በድህረ-ገጾችና በመጽሀፍም መልክ የሚጽፈው ኢትዮጵያዊ ምሁር የአገራችንን የፖለቲካ ሂደትና አውቃቀር ከኢምፔሪያሊስት ፕሮጀክት ውጭ ነጥሎ በማየት ነው ለመተንተንና ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያኖችን የሚያሳስተው። በመሆኑም በአገራችንም ሆነ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ያሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ጭራቆች ወይም አምባገነኖች፣ የካፒታሊስት አገሮች ፖለቲከኞች ደግሞ ቅዱሳንና ከደሙ ንጹሃን  ናቸው እየተባለ ነው ሀተታ የሚቀርበው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ አደገኛ ብቻ ሳይሆን በአገራችን ምድር ውስጥ ሁለንታዊ የሆነና ዕውነተኛ ሀብት ሊፈጠር የሚችልና ህዝባችንንም ከድህነት ሊያወጣው የሚያስችል ሳይንሳዊ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን ያግዳል። የወጣቱን አስተሳሰብ በማኮላሸት ዕውነትን ከውሸት ለመለየት እንዳይችል ያደርገዋል። ታሪክ ሰሪ ሳይሆን ተላላኪ በመሆን የአገራችንን ኋላ-ቀርነት የባሰውኑ ስር እንዲሰድ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት ሰላም እንዳይሰፍን፣ ህብረተሰብአዊ ፍቅር እንዳይኖርና ህዝባችንም አስተሳሰቡን በመሰብሰብና ኃይሉን በማጠናከር ወደ አገር ግንባታ ላይ እንዳያተኩር ይታገዳል። ከዚህ ስንነሳ ፖለቲካ ሳይንሳዊ ባህርይ ያለው ጽንሰ-ሃሳብ መሆኑን የመረዳቱ ችግር ስልጣን ላይ ባሉት ኃይሎች ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን በእኛ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ እንታገላለን በምንል ኃይሎችም ዘንድ ያለ ችግር ነው።

የካፒታሊስት አገሮችን ፖለቲካ እንመልከት። መሰረተ-ሃሳቡን ከሁለት አንፃር መመልከት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ወደ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነውንና ወደ ውጭ ደግሞ የሚካሄደውን ፖለቲካ። በመሰረቱ ስለ ካፒታሊስት አገሮች ፖለቲካ በምናወራበት ጊዜ ሰፋ ብሎ ከሚገኘው ምሁራዊ ኃይልና የሚዲያ ነፃነት ውጭ ነጥሎ ማየት በፍጹም አይቻልም። በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በተለይም የሲቪል ሶሳይቲ እየተባለ በሚጠራው ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖርም ሁሉም የሚስማሙበት ነገር ከዚህ የተሻለ ስርዓት እንደሌለና ይህንን የግዴታ መከላከል ያስፈልጋል በሚለው ላይ ነው። የተለያየ ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችንም ሁኔታና ፕሮግራምም በምንመረምርበት ጊዜ የተለያየ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ያላቸው ቢያስመስላቸውም፣ የሚስማሙበት ህገ-መንግስቱን መደገፍና መከላከል ያስፈልጋል በሚለው ላይ ነው። ስለሆነም ይህንን ወይም ያንን ስም ይዞ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ በምርጫ ጊዜ በአሸናፊነት ቢወጣም ስርዓቱን የሚቀናቀን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊያወጣና ተግባራዊ ሊያደርግ አይችልም። በተለይም ኒዎ-ሊበራሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ ሁሉም ፓርቲዎች፣ ሶሻል ዲሞክራቶች፣ ሶሻሊስቶች፣ ሊበራሎች፣ የክርሲቲያን ዲሞክራቲክ ወይም ኮንሰርቫቲቭ በመባል የሚታወቁ ፓርቲዎች በሙሉ በፖሊሲ ደረጃ እየተጠጋጉ መጥተዋል ማለት ይቻላል። ሊለያዩ የሚችሉት በአንዳንድ ጥቃቅን የማህበራዊ ነክ ጉዳዮች ላይ የድጎማ ገንዝብ እንጨምር አንጨምር በሚለው ላይ ብቻ ነው። ስለሆነም በመሰረቱ በተለያዩ ፓርቲዎች መሀከል መሰረታዊ የአስተሳሰብ ልዩነት የለም።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላና እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ተግባራዊ ይደረግ የነበረው በመንግስት የሚደገፍ የኢኮኖሚክ ፖሊሲ ወይም ኬይኔሲያን ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ነበር። በዚህ ፖሊሲ አማካይነትና፣ በልዩ ልዩ መልክ በሚገለጽ ጣልቃ-ገብነት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምክንያት የተነሳ ኢኮኖሚያቸው፣ እንፍራስትራክቸራቸውና ከተማዎቻቸው የወደሙባቸው እንደ ጀርመንና ፈረንሳይ የመሳሰሉት አገሮችና ሌሎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውን በአዲስ መልክ ያዋቅራሉ፤ ከተማዎቻቸውንና እንፍራስትራክቸራቸውን በመገንባት ሰፋ ላለ የምርትና የአገልግሎት ልውውጥ ሁኔታውን ያመቻቻሉ። በተለይም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምርምር ልዩ ትኩረትንና ድጎማን በመስጠት ዛሬ እንደምናየው ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ምጥቀት እየተደገፈ እንዲመረት ያደርጋሉ። ይህ ዐይነቱ የተወሳሰበ መንግስታዊ ድጋፍ ደግሞ የበለጠ ለኦሊጎፖሊስቶች ወይም ኢኮኖሚውን ለሚቆጣጠሩ ጥቂት ባለሀብቶች  በሩን በመክፈት የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ራሱን ችሎ(Autonomously)እንዲንቀሳቀስ አመቺ ሁኔታ ይፈጠርለታል። በተለይም ከ1970ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የመንግስት ሚና እየቀዘቀዘ ከመጣ ወዲህ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ የየመንግስታቱ መመሪያ ፖሊሲ በመሆን የካፒታሊስቶችን የበላይነትና በፖለቲካውም ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ከፍ እንዲል ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር፣ መንግስታት እስኪዚያን ጊዜ ድረስ ለማህበራዊ መስክና የስራ ዕድል ለመክፈት ያወጡ የነበረውን ገንዘብ በመቀነስና ለሀብታሞችም የቀረጥ ቅነሳ በማድረግ በደሃና በሀብታሙ የህብረተሰብ ክፍል መሀከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ ያደርጋሉ። ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የፊናንስ መስኩ ሚናው ከፍ እያለ በመምጣቱ ባንኮችና እንዲሁም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ከተጨባጭ ኢኮኖሚው ላይ ይልቅ የበለጠ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የአየር በአየር ንግዱን ያጧጡፉታል። የኢንዱስትሪዎች ምርት ክንዋኔ መቀዝቀዝና አዳዲስ መዋዕለ-ነዋዮች አለመካሄድ የስራ አጡን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ኃይል ሽግሽግና የፊናንስ ካፒታል ሚና ከፍ እያለ መምጣት የሰራተኛውን መደብ የመከራክር ኃይል እንዲዳከም ያደርገዋል። በመሆኑም ፖለቲካ  የሚባለው ሳይንሳዊ የአገር ማስተዳደሪያ መሳሪያ ከኃይል አሰላለፍ ለውጥ ጋር ባህርዩንና መልኩን እየቀየረ ይመጣል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በተለይም የሃይ ቴክ ኩባንያዎች፣ የሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብነትና፣(Military Industrial Complex) በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ጦርነትን የሚያስፋፉ ቲንክ ታንክ የሚባሉ የኒዎ-ኮም ድርጅቶች በአሉበት እንደ አሜሪካ በመሰለው አገር በመንግስትና በፓርቲዎች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ከፍ እያለ ይመጣል። በዚህም መሰረት የመንግስት ሚና የስራ መስክ የሚከፈትበትን ሁኔታ ከማመቻቸትና የማህበራዊ መስኩን ከመደጎም ይልቅ ሚናውን በማቀዝቀዝ በጦር መሳሪያ ምርት ላይ የበለጠ ያደላል። እንደዚህ ዐይነቱ የኃይል መሸጋሸግና፣ ትላልቅ ኩባንያዎችም ርካሽ የስራ ጉልበት ባለበት እንደ ሜክሲኮና ቻይና በመሳሰሉ አገሮች ኢንዱስትሪዎቻቸውን እየነቀሉ በመውሰዳቸው ሰራተኛውና መለስተኛ የከበርቴ መደብ (Middle Class)የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ይጠቃሉ። በዚህ መልክ በአንድ በኩል ሀብታሙ የበለጠ ሀብታም ሲሆን በሌላ ወገን ደግሞ የደሃው ቁጥር እየጨመረና ከዚህ ቀደም አነስተኛ ገቢ የነበረው የባሰ ደሃ እየሆነ ይመጣል።  ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ የኃይል ሽግሽግ በፖለቲካውም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማድረግ በየአራት ወይም በየስምንት ዐመቱ እንደየሁኔታው እየተፈራረቁ ስልጣንን የሚጨብጡት የሪፓብሊካንና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች በሎቢይስቶች ቁጥጥር ስር ይወድቃሉ።  በዚህ መልክ በኮንሰርቫቲቮችና በዲሞክራቶች መሀከል የሚካሄደው ትግልና የሚስተጋባው ፖለቲካ መሰረታዊ ልዩነት ባይኖረውም፣ የሪፓብሊካን ፓርቲው ኮንሰርቫቲቭ የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ በማጣመም የሚታገለው የበለጠ የትላልቅ ኩባንያዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በመሰረቱ የገበያን-ኢኮኖሚ መሰረተ-ሃሳብ የሚፃረር ነው።

በተለይም የጤና መስኩን ጠጋ ብለን ስንመለከት የሪፓብሊካን ፖርቲ ጥብቅናው ለኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ለፊናንስ ኢንዱስትሪው ነው ማለት ይቻላል። በተለይም ከኪሱ አውጥቶ ለመታከም የማይችለውን ሰፊ የአሜሪካ ህዝብ በመንግስት የተደገፈ የህክምና ድጎማ እንዳያገኝ መታገል የክርስትና ሃይማኖትን መሰረተ ሃሳብ የሚፃረር ነው።  የዚህ ዐይነቱ  የወገናዊነት ፖለቲካ ደግሞ ከአጭር ጊዜ አኳያ የተተለመ በመሆኑ ባለሀብታሞችን የባሰ ሲያደልብ ህክምና ማግኘት የሚገባውን ሰፊውን የአሜሪካን ህዝብ ደግሞ የባሰውኑ ይጎዳል። ይህ ሁኔታ የግዴታ ሊሰራ የሚችለውን ሰፊ ህዝብ ሲጎዳ በጠቅላላው ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ምርታማ ሊሆን የሚችለው የጤንነቱም ሁኔታ እንክብካቤ ካገኘ ብቻ ነው።  በሌላ ወገን ደግሞ እዚያው በዚያው የሪፓብሊካን ፓርቲውና ቲንክ ታንክ ድርጅቶች በአሜሪካን ምድር በንጹህ መልክ የሚካሄደው የገበያ ኢኮኖሚ ነው፤ ስለዚህም ሁሉም መወዳደር አለበት፤ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት የኢኮኖሚውን ሁኔታ ያዛባዋል በማለት ከተጨባጩ ሁኔታ የራቀ ቅስቀሳ ያስፋፋሉ። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ የመወዳደር ዕድል ያለው በማስመሰል ሰፊውን ህዝብ ያሳስታሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ መንግስት የሚያካሄደው ፖሊሲና ሰፊው የአሜሪካ ህዝብ በሀብት ክፍፍል ውስጥ ያለውን ቦታ ስንመለከት የፖለቲካውንም ሆነ የኢኮኖሚውን ሁኔታ ጥቂት ባለሀብቶች እንደሚወስኑ ማረጋገጥ ይቻላል። በተለይም ባለፈው ሰላሳ ዓመታት የካፒታሊስቶች ሚና እያየለ በመምጣቱና ለትምህርትና ሌሎች የሰፊውን ህዝብ ጭንቅላት ሊያዳብሩ በሚችሉ መስኮች ላይ የሚመደበው በጀት እየቀነሰ በመምጣቱ የአሜሪካን ካፒታሊዝም የበለጠ በቅራኔ እንዲዋጥና ሰፊው ህዝብም መብቱንና ግዴታውን ለማወቅ የማይችልበት ሆኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል። በአንፃሩ የአሜሪካ መንግስት ለመከላከያ ኃይሉና ለጦር መሳሪያ መግዣ በየዓመቱ 625 ብሊዮን ዶላር ያወጣል። ይህ የመከላከያ ባጀት ከራሺያው የመከላከያ ባጀት ጋር ሲወዳደር በ10 እጥፍ ይበልጣል። በዚህ ዐይነት የተዋቀረው መንግስትና የአገዛዙ ፖሊሲ በአጠቃላይ ሲታይ በህብረተሰቡ የህሊና አወቃቀር ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው።  የአመጽ መስፋፋት፣ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር መብዛት፣ አናሳ የሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መብታቸው እየተረገጠ መምጣቱ፣ ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው የአሜሪካን ፖለቲካ በብዙ ሺህ ማይሎች ከሳይንስና ከዲሞክራሲ ባህርይ እየተራራቀ እንደመጣ ነው። የዶናልድ ትረምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ የሚያረጋግጠው ከ60% በላይ የሚሆነው የአሜሪካን ህዝብ ሀቁን ከውሸት ሊለይ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ነው የሚያመለክተው። ሰሞኑን በአሜሪካዊው ፕሮፌሰር ጃሶን ብሬናን(Jason Brennan) ታትሞ በወጣው „ዲሞክራሲ አያስፈልግም“(Against Democracy) በሚለው መጽሃፋቸው ውስጥ መረዳት የሚቻለው የአሜሪካን ህዝብ ማንንና ለምን እንደሚመርጥ የተገነዘበ አለመሆኑን ነው። በሳቸውም አተናተን „ደንቆር ደንቆሮን ይመርጣል“ ፤ በመቀጠልም ይላሉ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ያልተገለጸለት ህዝብ „የራሱን ጥቅም የሚፃረር ፓለቲከኛና ፓርቲ ይመርጣል“  በማለት የአሜሪካ ህብረተሰብና የህዝቡ አስተሳሰብ ያለበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርገው ያስቀምጣሉ። ስለሆነም ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ አንድ ሰው ለምርጫ ከመቅረቡ በፊት ለዲሞክራሲ ብቃት ይኑረው አይኑረው ለማወቅ የግዴታ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ መፈተንና ፈተናውን ማለፍ እንዳለበት ያመለክታሉ። ይህ ዐይነቱ የፕሮፌሰር ብሬናን ጥናት በአውሮፓ ምድር ውስጥም በግልጽ ይታያል። በተለይም አብዛኛው ህዝብ ወደ ቀኝ እያደላና የፖለቲካ ማትሪክሱን እንዲለወጥ በማድረግ ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ የቀኝ አዝማሚያ እያየለ እንደመጣ እንገነዘባለን። ለዚህ ዐይነቱ አደገኛ አዝማሚያ ዋናው ምክንያት ሰፊው ህዝብ ራሱን በየጊዜው በአዳዲስ ዕውቀት ለማነጽ የሚያስችለው በቂ ጊዜ ስለማይኖረው ነው። በተጨማሪም የግል „ዜና“ ማሰራጫዎች እንደ አሸን መፍለቅና የሚሆነውን የማይሆነውን ማውራት የሰፊውን ህዝብ እየተፈታተኑና ንቃተ-ህሊናውን እያዳከሙት ነው። ስለሆነም ማስ ሚዲያዎች ማስተማሪያ ከመሆን ይልቅ ለመወዳደርና በማስታወቂያ አማካይነት ብዙ ገንዘብ ለማግኘትና የተመልካቹንም ቁጥር ለማሳደግ ሲሉ የህዝብን አዕምሮ በሚያሳስት ዜናዎችና ልዩ ልዩ ነገሮች ላይ ያደላሉ። በዚህም ምክንያት የሰፊው ህዝብ የማሰብ ኃይል እየቀነሰ መምጣቱን ጥናቶች ብቻ ሳይሆኑ ሁኔታዎችም ያረጋግጣሉ። አብዛኛው ህዝብም የየመንግስታቱን የውስጥም ሆነ የውጭ ፖለቲካ በደንብ ሊረዳ የማይችልበት ሁኔታ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። አንዳንድ ፖለቲከኞችም ሚዛናዊ የሆነ ትንተና ከመስጠት ይልቅ የመንግስታቸውን ፖለቲካ ትክክለኝነት ለማሳመን ሲሉ የተሳሳተ ኢንፎርሜሽን ወደ ውጭና በቴሌቪዢን ክርክሮች ላይ ያስተላልፋሉ፤ አጥብቀውም ይከራከራሉ። በተለይም የሶሪያንና የሊቢያን ጦርነቶች ዋና ምክንያት ለራሳቸው በሚስማማ መልክና በአንድ ወገን ብቻ በማቅረብ ህዝብን ያሳስታሉ።

ከዚህ ስንነሳ የካፒታሊስት መንግስታትና አገዛዞች በእርግጥ ሳይንስን ተከትለው ፖለቲካ የሚያካሂዱና ፖሊሲም የሚያወጡ ቢያስመስላቸውም፣ በሌላው ወገን ደግሞ በኃይል አሰላለፍ የተነሳና መንግስታትም የኢኮኖሚው ተጎታቾች በመሆናቸው ኢኮኖሚውን ከሚቆጣጠረው ውጭ ሌላ ፖሊሲና ፖለቲካ ሊከተሉ በፍጹም አይችሉም። በተለይም ከኢንዱስትሪዎችና ከባንኮች በሚመጣ ግፊት የተነሳ ሳይንሳዊና ህዝባዊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ የግዴታ የኢንዱስትሪ ባለሀብታሞችን የሚጠቅም ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ የሚፈጠርበትን ሁኔታ እያመቻቹ ነው። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ደግሞ የምርት ዋጋን ለመቀነስና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ነው ስለሚባል፣ በተለይም በአካባቢና በማህበራዊ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል። ስለሆነም ሳይንስና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ካፒታሊስቶችን ከመጥቀም ውጭ የሚካሄዱ አይደሉም። ይሁንና ስርዓቱ ውስጠ-ኃይሉ ከፍተኛ በመሆኑና በአንድ አገር ውስጥም በሁሉም ቦታዎች ተመሳሳይ ዕድገት ስላለ ቀውስ ቢፈጠርም እንደገና ኢኮኖሚው የማንሰራራት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። በተጨማሪም ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ በሲቪል ማህበረሰቡና በነቃው የህብረተሰብ ክፍል የሚደረገው ትግል ለፖሊሲ አውጭዎችና ለካፒታሊስቶችም በቀላሉ መፈናፈኛ አይሰጥም። ምሁሩም ራሱ በግራና በቀኝ፣ እንዲሁም በሰብአዊና በወግ አጥባቂዎች መሀከል የተከፋፈለ በመሆኑ የሚካሄደው ትግልና የሚቀርበው ጥናት በፖሊሲ አዎጭዎች ላይ የማይናቅ ተፅዕኖ አለው። በተለይም በጀርመን አገር የሀብት ክፍፍልንና ድህነትን አስመልክቶ በየሶስት ዓመቱ ጥናት ይቀርባል።

ከዚህ ወጣ ብለን የብዙ ካፒታሊስት አገሮችን፣ በተለይም የአሜሪካንን የውጭ ፖለቲካ በምንመለከበትና በምንመረምርበት ጊዜ ከሳይንስ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካን ኃያል መንግስት ሆኖ ሲወጣ የውጭ ፖሊሲው የበለጠ አግሬሲብና በተለይም የደካማ አገሮችን ብሄራዊ ነፃነት የሚቀናቀንና ቀጭጨው እንዲቀሩ የሚያደርጋቸው ሊሆን በቃ። በአሜሪካን ኤሊት ዘንድ ያለው ስምምነት ከአሜሪካን ፈቃድ ውጭ አንድ የሶስተኛው ዓለም አገር የራሱን ህብረተሰብ በፈለገውና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ማደራጀት የለበትም የሚል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካንን የሚቀናቀኑ ሌሎች ወደ ኃያልነት የሚያመሩ አገሮች ሁሉ መከበብና ከውስጥ ደግሞ በመረበሽ መበታተን አለባቸው የሚል ነው። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ በተለይም ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየና ለብዙ አገሮች መፈረካከስና ለብዙ መቶ ሺህ ህዝቦች መሞትና መሰደድ ምክንያት የሆነ በህይወታችን ያየነውና የምናየው ሀቅ ነው። ዩጎዝላቪያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያና ሶሪያ የዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ሰብአዊ ፓለቲካ ሰለባዎች ናቸው። አሜሪካ ይህ ዐይነቱን አደገኛና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲናጋ ለአገዛዙ የተሳሳተ ኢንፎርሚሼን የሚያቀብሉ እንደ ሲ አይ ኤ የመሳሰሉ የስለላ ድርጅቶች አሉ። ከዚህም ሌላ በአሜሪካ ምድር ውስጥ በተጨማሪ 17 የስለላና የሰላም ጠንቅ ድርጅቶች አሉ። አገሮችን ለመሰለልና በተለይም በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ አለመረጋጋት እንዳይኖር የሲ አይ ኤና(CIA) የተቀሩት የስለላ ድርጅቶች ሚና የየአገሩን መንግስታት ቢሮክራቶች መመልመልና ኢንፎርሜሽን እንዲያቀብሉ ማድረግ ነው። ከዚህ አጭር ትንተና ስንነሳ የምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ወደ ውስጥ የሰለጠነና በሳይንስ የተደገፈ ፖለቲካ ተግባራዊ የሚያደርግ ቢያስመስለውም፣ ወደ ውጭ የሚያካሂደው ፖሊሲና ፖለቲካው ስልጣኔ የጎደለው፣ የተቀረውን የዓለም ህዝብ በነፃነት ዓለም እንዳይኖር የሚያደርገው፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆን የሚያግደው፣ ባህልን በማዳበር ወደ ውስጥ ህብረተሰብአዊ ስምምነት እንዳይፈጠር የሚያደርግና፣ የአንድ አገር ህዝብም በዘለዓለም የዝቅተኝነት ስሜት እንዲኖር የሚያደርግ እጅግ አደገኛ ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል። እንደምናየው የዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ ውጤት በየአገሩ ጦርነት በማካሄድ ህዝቦችን ሲያፈናቅል፣ እነዚህ የሚፈናቀሉ ህዝቦች ደግሞ ወደ ካፒታሊስት አገሮች እየተሰደዱ በመምጣት ለተነሳው የቀኝ አዝማሚያ እንደ ዋና ምክንያት እየቀረቡ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት  የካፒታሊስት አገሮች ፖሊሲ መሆኑን አብዛኛው ህዝብ የሚረዳው አይደለም።

በአጠቃላይ ሲታይ ይህ ዐይነቱ አግሬሲቭ ፖሊሲ የግሪክ ፈላስፎች፣ የሬናሳንስ ምሁሮችና፣ በተለይም የጀርመን ክላሲኮች በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ያዳበሩትንና ያስተማሩትን የሰብአዊነትና በአገሮች መሀከል ሊኖር የሚገባውን መከባበር የሚቀናቀን አደገኛ አካሄድ ነው። ስለሆነም ነው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ሰላም ሲሰፍን በአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ በጎሳና በሃይማኖት ተሳበው ጦርነት እንዲካሄድ የተደረገውና የሚደረገው። በሌላ አነጋገር፣ የጦር መሳሪያዎች ሙከራ በመሆንና መሬታችንና ህዝባችንን የጦር መሳሪያዎች መሞከሪያ እንዲሁኑ በማድረግ ፍዳችንን እንድናይ የተደረገው በዚህ ዐይነቱ አግሬሲብ ፖለቲካና በእኛ ድንቁርና የተነሳ ነው። ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ በመነሳት ነው የካፒታሊስት አገሮችን ፖለቲካ መረዳትና መተንተን የምንችለው። ስለሆነም በሁሉም የካፒታሊስት አገሮች ያለው የፖለቲካ ስምምነት(Political Consensus) የምዕራቡ „የፖለቲካ እሴት“ ነው ትክክለኛው፣ ሁሉም አገሮች ይህንን በምዕራቡ የተደነገገውን ፖሊሲ መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው በማለት እያንዳንዱ አገር ከራሱ ታሪክ፣ ባህል፣ የህብረተሰብ አወቃቀር፣ የስነ-ልቦናና የህዝብ ፍላጐት ሁኔታ በመነሳት የየራሱን ብሄራዊ ፖሊሲ መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ የሚገባው ሳይሆን የግዴታ “የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲውን“ ድንጋጌ መቀበልና በመጀመሪያ ደረጃ ሽብርተኞችን መዋጋት ነው የሚል ነው። ይህንን የሚቃውምና የራሱን ፖሊሲና ፖለቲካ የሚከተል በሙሉ አፈንጋጭ ነው እየተባለ ጦርነት ይታወጅበታል። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ የሶስተኛው ዓለም አገዛዝ የፈለገውን ያህል ጨፍጫፊና ሀብት ዘራፊ ቢሆንም  የካፒታሊት አገሮችን ጥቅም እስካልተጋፋ ድረስ ዝም ብሎ ነው የሚታለፈው። በአገራችን የምናየው ይህንን ሀቅ ነው።

   የአገራችን ዋናው የፖለቲካ ችግር-በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ባህል አለመኖር ነው !

በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንድ የተለመደና ከሳይንስና ከህብረተሰብ ዕድገት ታሪክና የባህል ምርምር ዘዴ ጋር ሊጣጣም የማይችል አነጋገር አለ። በመጀመሪያ ደረጃ በሁላችንም ዕምነት ዛሬ በአገራችን ያለው ድህነት፣ ረሃብ፣ የከተማዎች መዝረክረክ፣ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝባችን ከማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የአኗኗር በታች መኖር ከአስተሳሰብ ድህነት ጋር ሊያያዝ የሚችል አይደለም የሚል ነው። ስለሆነም ዛሬ በአገራችን ምድር አፍጦ አግጦ የሚታየው ሁኔታ ዛሬ የተፈጠረ ነው። ሁለተኛውና ትልቁ ስህተት፣ ታሪካችንን ከሚገባው በላይ አጉልቶ ማስቀመጥ ነው። በተለይም ይህ ዐይነቱ ታሪክን አጉልቶና ከሌሎች አብልጦ ማየት ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ህብረተሰብአችን ያሳለፈውን „የዕድገት ጎዳናና“ አስቸጋሪ ሁኔታ በቅጡ እንዳናይ አግዶናል። በሌላ ወገን ደግሞ እኔ እስከማውቀው ድረስ አነሰም በዛም ታሪክ የሌለው ህዝብ የለም። ይሁንና ግን ታሪክን ታሪክ የሚያስብለው አንድ ህዝብ ራሱን መለወጥ ሲችልና፣ ከእንስሳ የተለየ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው። ይህንን ከቁጥር ሳናገባና ታሪክ የሚባለውን ነገር ከሌሎች የጭንቅላትና የህብረተሰብ ክንውኖች፣ ማለትም ባህላዊ ለውጥ፣ ሳይንሳዊ ግኝትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ እንዲሁም የከተማዎች በዕቅድ መስራት ጋር ነጥለን አውጥተን ታሪክ ነበረን፣ መሪዎቻችንም ታሪክን ሰርተዋል ብለን ዝም ብለን የምንናገርና የምንጽፍ ከሆነ በተለይም ታዳጊውን ትውልድ እንዳይጠይቅና እንዳያስብ ነው የምናደርገው። የሚወጡት ሙዚቃዎች፣ የታሪክ አጻጻፎችና ግጥሞች በሙሉ ከነበረውና ካለው ሁኔታ፣ እንዲሁም ካለፈውና ከአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የማይደረሱ፣ የማይቃኙና የማይጻፉ በመሆናቸው ህዝባችንና አገራችን ለአሉበት የተወሳሰቡ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደመፍትሄ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። በተለይም አንድ አገር እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ ሁኔታውን በማገናዘብ የማይደረስ ጽሁፍ፣ የማይሳል ስዕልና የማይቃኝ ሙዚቃ ህዝባችንና የገዢው መደብ፣ እንዲሁም ሌላው ኤሊት ያሉበትን ቦታ እንዳያውቁ ይደረጋቸዋል። እንደዚህ ስል ድርጊቶችን በሙሉ መናቄ ወይም እንዳልነበሩ መቁጠሬ አይደለም። የበለጠ በተነፃፃሪ የምርምር ዘዴ(Comparative Studies) እያወዳደርን ለመመራመርና ለመጻፍ ከቻልን ዛሬ ላለንበት ችግር ዋናውን ምክንያት ማግኘታችን ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሄም ማግኘቱ ይቀለናል ከሚለው አስተሳሰብ በመነሳት ነው። ይህንን ማድረግ የምንችለው ደግሞ የምንፈልገውን ካወቅን ብቻ ነው። በዚህ መልክ ሙከራ ካደረግን ከሚያወዛግቡና ከሚያጣሉን ነገሮች ተላቀን የበለጠ ወደ ሳይንሳዊ ምርምር ላይ ማድላት እንችላለን።

ይህንን መሰረት አድርገን ስንነሳ በአጠቃላይ ሲታይ የአገራችንን ዕድገት የሚያፋጥኑ፣ የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ፣ በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ጥሬ-ሀብቶችን አውጥቶ መለወጥና መጠቀም፣ የዕደ-ጥበብ ስራንና ንግድን ማስፋፋት፣ ከዚህም በላይ ከተማዎችንና መንደሮችን በዕቅድ መቆርቆርና መገንባት፣ እነዚህን ሁሉ በሳይንሳዊ ግኝት ማሻሻሉ ባህላችን አልነበሩም ብዬ ብናገር ተራ ውንጀላ ወይም ደግሞ ታሪክን እንደ ማንኳሰስ እንደማይቆጠርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በህብረተሰብ የዕድገት ታሪክ ውስጥ እንደ ተረጋገጠው በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሁኔታዎች ተሻሽለው ሲገኙ ብቻ ነው ፈላስፋዎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎችና የቴክኖሎጂ ሰዎች ብቅ በማለት ለነበረው ዕድገት ልዩ እምርታንና መሻሻልን የሚሰጡት። ከዚህች አጠር ያለ ሀተታ ስንነሳና አሁን በቅርቡ የአርኪዎሎጂና የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ በሆኑት በዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ ለኢሳት ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ሰፋ ያለና የሚያመረቃ ማብራሪያ መሰረት አገራችን በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የህዝቧን የኑሮ ደረጃ ሊያሻሽል የሚችል ዕውቀት፣ ቢያንስ በቤተክርስቲያን ደረጃ ሊስፋፋ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የሚሳሉትም ስዕሎች የህዝቡን የአኗኗር ሁኔታ የሚያንጸባርቁ ሳይሆኑ በቀጥታ ከሃይማኖት ጋር በመያያዘቸው  ለኋላ-ቀርነታችን ምክንያት እንደሆኑ ነው።  በሌላ ወገን ደግሞ ምሁሩ በደንብ እንዳስገነዘቡት በአውሮፓ ምድር ቤተክርስቲያንና ሃይማኖት ሰፋ ያለ የዕውቀት መመራመሪያ መድረኮች እንደነበሩ ነው። በእርግጥም አብዛኛዎቹ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች የካቶሊክ፣ በኋላ ደግሞ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። በተጨማሪም ሃይማኖትንና ፍልስፍናን ለማገናኘት ወይም ለማዛመድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ አብዮታዊ የሚባሉ የአስተሳሰብ ለውጦች ሊመጡ የቻሉት ከራሱ ከሃማኖት ተከታዮች ወይም ከቄሶች ነው። ለምሳሌ ማርቲን ሉተርና ተከታዮችን መመልከቱና በእነሱ ትምህርት መሰረት የአውሮፓ ህዝብ ከተኛበት እንደነቃ መገንዘብ እንችላለን። በቃለ-ምልልሱ ያልተብራራ ነገር፣ ለምሳሌ የአውሮፓን የህብረተሰብ ታሪክ ስንመለከት ዕውቀት የሚባለው አጠቃላይ ነገር ከውጭ የመጣ ሲሆን ከውስጥ ውስጣዊ-ኃይል(Dynamism)በማግኘትና በመዳበር እንዲሁም በመፈተሽ ለህብረተሰብአዊ ለውጥ አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ ነው። ወደ አገራችን ስንመጣ በንግድና በምሁራን እንቅስቃሴ አማካይነት ከውጭ ዕውቀት ባለመምጣቱና፣ አገራችንም ከአንድ ሺህ ዐመት በላይ ከግሪኩ ስልጣኔ፣ በኋላ ደግሞ ከአውሮፓው የሬናሳንስና የተገለጸለት እንቅስቃሴ ጋር የመተዋወቅ  ዕድል ባለማግኘቷ የህዝባችን አኗኗርና የአመራረት ሁኔታ ሊለወጥ አልቻለም። ስለሆነም ህዝባችን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅና የማዳበር ችሎታ አልነበረውም።  በተጨማሪም በተለያዩ መልኮች ሊገለጽ የሚችል ምሁራዊ ኃይል ብቅ ለማለት ባለመቻሉ ስርዓቱን ሊጋፈጠው አልቻለም። አገዛዙም አዳዲስ ነገሮችን ማየት ስላልቻለ ራሱንና የገበሬውን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህብረተሰብአችን ተመራማሪዎችንና በትችታዊ መልክ ጥያቄ እያቀረቡ የህዝቡን አኗኗር መተቸት የሚችሉ ምሁሮች ባለመፈጠራቸው አገራችንና ህዝባችን ካሉበት የኑሮ ደረጃ ወደ ተሻለ መሸጋገርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር አልቻሉም።  ይህ በራሱ ደግሞ የፖለቲካው ስርዓት በዚያው ፈርጥሞ እንዲቀር በማድረጉ ከላይም ሆነ ከታች መሻሻል አልነበረም። የመንግስትና የፖለቲካ ቲዎሪም ሊፈልቅና ሊዳብር ባለመቻሉ በተለያየ ጊዜ ብቅ ያሉና ህዝቡን ይገዙ የነበሩ መሪዎች በአቦ ሰጡኝ የሚራመዱ ነበሩ ማለት ይቻላል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ያልተዘበራረቀ፣ በተለያየ የስራ-ክፍፍል ያልተደራጀና ያልተሰማራ፣ በገጠርና በከተማ መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ ክፍፍል የሌለበት፣ የዕደ-ጥበብ ሙያና የንግድ እንቅስቃሴ የማይታወቅበት ስርዓት ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።  ይህ ሁኔታ በተለይም ኢትዮጵያ ወደ አጠቃላይ አገዛዝ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ስትሸጋገር መሰረታዊ ለውጥ ያየ አልነበረም። በአንፃሩ የካፒታሊዝም ወደ አገራችን መግባት ሁኔታውን የባሰ አዘበራረቀው እንጂ። ውሰጣዊ-ኃይሉም ከፍ ያለና የማሰብ ኃይሉም የዳበረ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል ባለመቻሉ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ፣ በሁሉም መልክ በሚገለጽ ወደ ህብረ-ብሄር መሸጋገር አልቻለችም። በሌላ አነጋገር፣ በኢትዮጵያ ምድር የማዕከላዊ ግዛት አወቃቀር ወይም ወደ ህብረ-ብሄር መሸጋገር ከላይ በተዘረዘረው ምክንያት የተነሳ የአውሮፓውን መንገድ የያዘ አልነበረም ማለት ይቻላል። ይህም ማለት፣ በተለያዩ ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ ከተማዎችና መንደሮች  በደንብ መገንባት አለባቸው፤ ኢንስቲቱሽኖች መቋቋም አለባቸው። በዚህም አማካይነት የስራ-ክፍፍልና ንግድ መዳበር አለባቸው። ከዚህም በላይ በክፍለ-ሀገሮች መሀከል ህዝቡ ከአንዱ ክፍለ-ሀገር ወደ ሌላው በመንቀሳቀስ ንግድና ሌሎች ነገሮችን ለማካሄድ ቢያንስ የባቡር ሃዲድ ግኑኝነት መኖር አለበት። በዚህ መልክ ብቻ የሃሳብና የልምድ ልውውጥ መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን አንዱ የብሄረ-ሰብ ክፍል ሰው ከሌላው ጋር በመጋባትና በመዋለድ ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ኃይል ይፈጠራል። የፈጠራ ችሎታ ይዳብራል።  እንደዚህ ዐይነቱ መተሳሰርና በንግድ አማካይነት መገናኘት የህብረ-ብሄርን ግንባታ ያቃልላል፣ የህዝቡም ብሄራዊ ስሜት ይዳብራል። ይህ በራሱ ሄገል እንደሚያስተምረን ለሲቪል ማህበረሰብ መፈጠር ያመቻል። ከዚህ ስንነሳ ነው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደትና የአገራችንን ወደ ኋላ-መቅረት መረዳት የምንችለው። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ ሳይንሳዊ የፖለቲካ አስተዳደርና ትችታዊ አመለካከት ሊዳብር የሚችለው ይህንን ጉዳይ ከሌሎች ነገሮች ጋር በማያያዝ መመርመር የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ እስከ 1974 ዓ.ም ድረስና እስከዛሬም ድረሰ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ፣ መንግስታዊ አወቃቀርና የፖለቲካ አስተዳደር ኢ-ሳይንሳዊ ነው። የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የተከተለ አይደለም። የተፈጥሮን ህግ የሚቀናቀን የፖለቲካ አውቃቀር ነው በአገራችን ምድር የተለመደውና እስከዛሬም ድረስ ትርምስ ውስጥ ከቶን ወደፊት አላራምደን ያለው። አፄ ኃለስላሴና አገዛዛቸው የሳይንስና የፍልስፍና ሰዎች ስላልነበሩ ነው አገራችንን ጥበባዊና ስነ-ስርዓት ባለው መልክ መገንባት ያልቻሉት። ስለሆነም በእሳቸው አገዛዝ ዘመንም ውስጠ-ሃይሉ የዳበረና የፖለቲካ ስልጣንን ሊረከብና አገራችንን በሁሉም መልክ ዘመናዊና ጥበባዊ ሊያደርጋት የሚችል የተማረና የነቃ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል አልቻለም። በእሳቸው ዘመን ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብሄራዊ ስሜት የሌለውና በዲሲፕሊን ሊሰራ የማይችል ኃይል እንዲፈጠር ከማድረጉ በስተቀር ህዝባችንን ሊሰበስብና የፈጠራ ችሎታውን ሊያዳብር የቻለ የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። ሁኔታዎችና ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ለመፍጠር አለማስቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ እዚያው በዚያው የፖሊሲው ክስተት የሆኑ፣ እዚህና እዚያ ተሰበጣጥረው የሚገኙ ለብሄራዊ ሀብትና ብሄራዊ ባህል መዳበር የማይጠቅሙ የኢኮኖሚ መሰል እንቅስቃሴዎች በመስፋፋት የህዝባችንን አስተሳሰብ ለማዘበራረቅ ችለዋል። እነዚህ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በኢንፎርማል መስክ የሚገለጹና እርስበርሳቸው ያልተያያዙ፣ ከእጅ ወደ አፍ(Subistence Economy) የሚካሄድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በእነዚህ መስኮች ውስጥ በቂ ትርፍ ምርት(Surplus prodcut) ማምረት ስለማይቻል በገበያ ላይ የሚቀርበው ምርት እያደገ የመጣውን ህዝብ ቁጥርና ፍላጎቱን የሚያሟሉ አልነበሩም፤ አይደሉምም።

የተማሪው እንቅስቃሴና የፖለቲካ ግንዛቤው !

በጊዜው የተነሳው የተማሪው እንቅስቃሴ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን ከህብረተሰብአችን የፈለቀ ነው። እንዲሁም በኋላ የማርክሲዝምን ሌኒንዝምን መመሪያ ይዘው ብቅ ያሉት ድርጅቶች እንዲሁ ከላይ የተወረወሩ ሳይሆኑ ከፊዩዳሉ ህብረተሰብ ብቅ ያሉና ዘመናዊ ከሚባለው ትምህርት ጋር የተዋወቁ ናቸው። እንዲያው ገርደፍ ገርደፍ አድርጎ የህብረተሰባችንን አወቃቀር፣ የስነ-ልቦና ወይም የህሊና ሁኔታ ለተመለከተ የአብዛኛው ህዝብ ግኑኝነትና አስተሳሰብ ፊዩዳል በሚባለው አስተሳሰብ የሚገለጽና፣ በአጠቃላይም ሲታይ ህዝባችን ፖለቲካ የሚባል ባህል አልነበረውም። በአገራችንም የፊዩዳል ታሪክ ውስጥ ፊዩዳላዊ ስርዓቱን የሚቀናቀን አስተሳሰብ ብቅ ያለው በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በ60ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ነው ማለት ይቻላል። በአንፃሩ ግን በአውሮፓ ምድር ውስጥ የፊዩዳሉን ስርዓት መቃወምና ብዝበዛም እንዲቀነስ መጨቅጨቅ የተጀመረው በ15ኛው ክፍለ-ዘመን ሲሆን፣ በግሪክ ደግሞ በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። ይህም ማለት በአውሮፖ ውስጥ ህዝቡ ለመብቱ ጥያቄ ሲያቀርብና በጊዜው የነበረውን ስርዓት ሲጋፈጥ እኛ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በእንቅልፍ ላይ ነበርን ማለት ነው።  ወደ ህብረተሰብና ወደ ቤተሰብም ግንኙነት ስንመጣ የርስ በርሱ ግኑኝነት በፊዩዳሉ ባህል የሚገለጽ እንጂ ፖለቲካን አስመልክቶ የመወያየት፣ የመከራከርና ጥያቄ የመጠየቅ ባህል አልነበረም፤ ወይም የተለመደ አልነበረም። እንደዚሁም በልጆችና በወላጆች መሀከል የነበረው ግኑኝነት ልማዳዊ የነበረና፣ በጊዜው ሰፍኖ የነበረውን ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት የሚያንጸባርቅ ነበር። በባልና በሚስት መሀከል የነበረውን ግኑኝነት ስንመለከትም፣ በተለይም የፊዩዳል ቤተሰብ ውስጥ ሚስቶች ባሎቻቸውን አንቱ የሚሉበት ሁኔታ ነበር። በመሀከላቸውም ሃሳብ ለሃሳብ የመለዋወጥ፣ የመመካከርና አይሆንም የሚባል ነገር አልነበረም። ባል አምሽቶ ሲመጣ የት ዋሉ ሳይባል ምግብ ቀርቦለት ተበልቶ ይተኛል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለብዙዎች አስር ዐመታት በተደጋጋሚ የተለመደና ስር የሰደደ በመሆኑ እንደ ተፈጥሮአዊ የተወሰደ የአኗኗር ስልት ነው። ይህ ማለት ግን ባል የፈለገውን ያደርጋል ማለት አልነበረም። ለማለት የምፈልገው እንደዚህ የተዘጋና የሃሳብ መለዋወጥ ያልተለመደበትና ጥያቄ ለማቅረብ የማይችል ህብረተሰብ በጊዜ ብዛት ምክንያት የተነሳ የማሰብ ኃይሉ ከመዳበር ይልቅ እዚያው ባለበት ይረግጣል። የራሱንም ሁኔታ ለማሻሻል ያለው ኃይል በጣም ዝቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በተፈጥሮ ውስጥ በሚከሰቱ አደጋዎች የመጎዳት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። መንደሮችና ትናንሽ ከተማዎች በስነ-ስርዓት ባለመሰራታቸውና፣ የህዝቡንም የማሰብ ኃይል የሚያዳብሩ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በየቦታው ስላልነበሩ፣ የነበሩትም የማሰብ ኃይልን ለማዳበር የሚጠቅሙ ባለመሆናቸው ይህ ሁኔታ ያለውን ፊዩዳላዊ የርስ በርስ ግኑኝነት የባሰ አጠነከረው። እንደዚህ ያለው የአኗኗር ስልትና ህሊናዊ አወቃቀር እስከ 1974 ዓ.ም ድረሰ የቆየና ለጠቅላላው ህዝባችን የኋላ-መቅረት ዋናው ምክንያት የሆነ ነው። ተማሪው እንቅስቃሴውን ሲጀምር ይህንን የመሰለውን ፊዩዳላዊ የርስ በርስ ግኑኝነት በህብረተሰቡ የማሰብ ኃይል ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በደንብ ያጥና አያጥና የሚታወቅ ነገር የለም። ማለት የሚቻለው ግን የተማሪው እንቅስቃሴ የማርክስን የማቴሪያሊስት ቲዎሪ ብቻ በመረዳቱ፣  በጊዜው ሰፍኖ የነበረው የፊዩዳል ስርዓት ከተገረሰሰ የአስተሳሰብ ለውጥም ሊመጣ ይችላል ብሎ በመገመቱ የአስተሳሰብና ወይም የህሊና-አወቃቀርን ጉዳይ በሚመለከት ጥናት ያደረገ አይመስለኝም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ እንዳየነው የራሱን የሆነ አሉታዊ ሁኔታ ሊፈጥር ቻለ። በቂና የጠለቀ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ምርምር እንዳይካሄድ አገደ።

በአንፃሩ የማርክሲዝምን አስተሳሰብ ዕድገትና የማርክስን የህይወት ታሪክ ላነበበ ማርክስና አስተሳሰቡ የአውሮፓው የምሁር እንቅስቃሴና የካፒታሊዝም ዕድገት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ማርክስ በንጹህ መልክ በሚገለጽ በፊዩዳል ስርዓት ውስጥ ቢወለድ ኖሮ እንደዚያ ዐይነቱን በተለይም ዳስ ካፒታልንና መሰረታዊ ጽሁፎችን(Ground Work) ሊጽፍ አይችልም ነበር። ማርክስ በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ ተወልዶ ያደገ ብቻ ሳይሆን በጥልቀት ከግሪኩ ፍልስፍና ጋር የተዋወቀ ነበር።  የዶክትሬት ስራውንም የጻፈው የዴሞክሪቲክንና የኢፒኩሪያን ፍልስፍና በተፈጥሮ ላይ ያላቸውን አመለካከት(The Difference between the Democritean and Epicurean Philosophy of Nature) በማነፃፀር ነው። በተጨማሪም የተፈጥሮ ሳይንስን መጽሀፎች ያነበበና የተመራመረ ነበር። የሼክስፒዬርንም የድራማ ስራዎች የሚያደንቅ ነበር። ስለዚህም ዝም ብሉ ዳስ ካፒታልን የጻፈና የማይሆን ነገር ያስፋፋ ሳይሆን በጊዜው ከነበረው እያደገና እየተወሳሰበ፣ ይሁንና ደግሞ የሰፊውን ህዝብ በተለይም የወዝአደሩን ኑሮ ለማሻሻል ያልቻለውንና በከፍተኛ ደረጃም ይበዘብዝ የነበረውን ስርዓት ስለተመለከተና ቢያንስ ከሰላሳ ዐመት በላይ ካጠናና ከተመራመረ በኋላ ነው። ፍሪድሪሽ ኤንግልስም እንደዚሁ በጥልቅ የተመራመረና ራሱ የፋብሪካ ባለቤት ልጅ በመሆኑ በጊዜው ካፒታሊዝም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ለማለት የምፈልገው፣ ሰውን ለማሳሳት ወይም በመጥፎ አስተሳሰብ በመገፋት የጻፉት ሳይሆን በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በደንብ ካጠኑ በኋላ ነው እንደዚያ ያለውን ሀተታ መጻፍ የቻሉት። የማርክስ ዳስ ካፒታልም እስካሁን ድረስ ጊዜያዊነቱን ያላጣና ስለ ኢኮኖሚክስ ከተጸፉት ስራዎች በሙሉ የላቀና፣ በራሳቸው በከበርቴው ክሪቲካል ኢኮኖሚስቶችና የህብረተሰብ ተመራማሪዎች በእነ ሹምፔተር ሁሉ የተረጋገጠና ተቀባይነትን ያገኘ ስራ ነው። ስለዚህም በአብዮቱ ወቅት በአገራችን ምድር ስለተከሰተው የማያስፈልግ መጋጨትና ርስ በርስ መገዳደል ማርክስና ስራዎቹን ተጠያቂ ልናደርጋቸው በፍጹም አንችልም። ከላይ በሰፊው ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ ሊገለጽ የሚችል ምሁራዊ እንቅስቃሴና የፖለቲካ ክርክርና ውይይት ባለመኖሩ የተወሰነው የተማሪው እንቅስቃሴ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በጊዜው የተነሳውን ትክክለኛ ጥያቄ ወደማይሆን አቅጣጫ እንዲሄድ በማድረግ ራሱ በበኩሉ ረጋ ያለ ጥናትና ምርምር እንዳይኖር አገደ። በጊዜውና በኋላም ለተፈጠሩት ምስቅልቅል ሁኔታዎች መፍትሄ ለማፍለቅ አልተቻለም። ሁሉም ደሙ የፈላና ልቡ ያበጠ በመሆኑ በጊዜው የተነሳውን እንቅስቃሴና በምድር ላይ ይታይ የነበረውን ችግር በጉልበት የሚፈታ ነበር የመሰለው። እስካሁንም ድረስ ያለው ችግር ይህ ነው። ስለሆነም በአብዮቱ ወቅት በተፈጠረው ውዝግብና የፖለቲካ ውዥንብር የተነሳ አያሌ አሉታዊ ኃይሎች(Negative Forces) በመፈጠር እስከዛሬም ድረስ የፖለቲካውን መድረክ ያዋክቡታል። ሁላችንም ፖለቲካ የሚለውን ትልቅና ሳይንሳዊ ጽንሰ-ሃሳብ ለመረዳት ስላልቻልን ግራ ተጋብተን እንገኛለን። የሚያስተምረንም ባለመኖሩ ሁሉም በየፊናው ፖለቲከኛ ነኝ እያለ መቀመጫና መቆሚያ አሳጥቶናል።

ሌላው የኛ አገር ችግር በተለይም ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የተስፋፋው ትምህርት በአስተሳሰብ አላበለጸገንም። በረቀቀ መልክና አርቀን እንድናስብም አላደረገንም። ለምሳሌ ዘግየት ባለው የማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን(Late Middle Ages)በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት አለፍ አለፍ ብለን ስንመለከት ካለምክንያት አይደለም በአንድና በሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ያህንን ያህል ሳይንቲስቶች፣ ፈላስፋዎች፣ የማቲማቲክስ ተመራማሪዎች፣ የድራማና የስነ-ጽሁፍ ሰዎች፣ ከዚያም በላይ የአርክቴከቸር ምሁሮችና ሰዓሊዎች እንደ አሸን ሊፈልቁ የቻሉት። ለምሳሌ የጆን ስትዋርት ሚልን የህይወት ታሪክ ስንመለከት አስገራሚ ነገር እንማራለን። አባቱ ጄምስ ሚል የእነ ጆን ሎክንና የጄሬ ቤንትሃምን የፍልስፍና አመለካከት የሚከተል ነበር። በሁለቱ ፈላስፋዎች ዕምነት የአንድ ልጅ አዕምሮ በህፃንነቱ ምንም እንዳልተጸፋበት ነጭ ወረቀት ዓይነት ነው። ስለሆነም የስትዋርት አባት ይህንን አመለካከት መሰረት በማድረግ ራሱ ቤት ውስጥ ያስተምረዋል። የሚሆን የማይሆን ነገር እንዳይማር ከሌሎች ልጆች ጋር እንዳይገናኝ ያደርገዋል። በመሆኑም ጄምስ ሚል ልጁን ስትዋርት ሚልን ሶክራቲያዊ በሆነ መንገድ ያስተምረዋል። ይህም ማለት ዝም ብሎ ሽምደዳ ሳይሆን በመጠየቅና፣ ካልገባው ደግሞ መላልሶ በመሰቀልኛ መንገድ በመጠየቅ ልጁ የዓለምን ሁኔታ እንዲረዳ ያደርገዋል። በዚህ መልክ ትምህርት የቀሰመው ስትዋርት ሚል በተወለደ በሶስት ዓመቱ ከግሪኩ ፍልስፍና ጋር በደንብ ይተዋወቃል። ስድስት ዐመት ሲሞላው የሮማውያንን ታሪክ ይጽፋል። በሰባት ዐመቱ የፕላቶንን ውይይት እንዳለ በኦሪጂናል መልኩ ይረዳል። በስምንት ዐመቱ የላቲን ቋንቋን ይማራል። በ12 ዐመቱ ከኢኮኖሚክስ፣ ከታሪክና ከፖለቲካ ዕውቀት ጋር ይተዋወቃል። በዚህ ዕድሜው የተወሳሰቡ የሂሳብ ጥያቄዎችን መፍታት መቻሉ ብቻ ሳይሆን በሳይንስ ላይ የጠለቀ ምርምር ያደርጋል። በ20 ዐመቱ እንግሊዝ አገር አሉ ከሚባሉት ታዋቂ ምሁራንና ተመራማሪዎች ውስጥ አንዱ ነበር። ይሁንናም ከጄሪ ቤንትሃም ፍልስፍና ጋር ቢተዋወቅምና አባቱም የቤንትሃም ጓደኛ ቢሆንም፣ ስትዋርት ሚል ግን ሙሉ በሙሉ በቤንትሃም  የዩሊታሪያን አስተሳሰብ የሚስማማ አልነበረም።  ሚል ወደ አንድ የሚያስደስት ነገር ወይም ርካታ የሚሰጥ ዓላማ ለመድረስ ትክክለኛ አካሄድን መከተል ያስፈልጋል በሚለው  በቤንትሃም አባባል ቢስማማም፣ በሌላ ወገን ግን በአጠቃላይ አነጋገር ቤንትሃም ከፍተኛ ደስታ በሚለው አስተሳሰቡ ላይ የሚስማማ አልነበረም። ስለሆነም ስትዋርት ሚል የራሱን የደስተኝነት ቲዎሪ አዳበረ። በዚህም መሰረት ከፍ ያለና ዝቅ ያለ ደስተኝነት እንዳለ አመነ። ይህም ማለት አንድ ሰው ለመደሰት ሙሉ በሙሉ ከፍተኛውን ደስታ ወይም በከፍተኛ ቁጥር የሚለካን ነገር ማግኘት የለበትም በማለት ተከራከረው። በስቴዋርትም ዕምነት በቀላሉ ከሚረካ ሞኝ ሰው ይልቅ በማይደሰተው ሶክራተስ መስማማቱ የተሻለ ደስተኝነትን ማግኘት እንደሚቻል አረጋገጠ። በዚህ መልክ የሰለጠነውና ጭንቅላቱ የተቀረጸ የወጣለት ሊበራልና አጥብቆ አምባገነን ወይም ዲስፖቲያዊ አገዛዝን የሚቃወም ነበር።  እሱ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለውም ሆነ በሱ ጊዜ፣ በኋላም የተወለዱት የአውሮፓ ታላላቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም የሰብአዊነት ተሟጋቾችና የዕድገት ፈለግ ቀያሶች በዚህ ዐይነት የዕውቀት አካሄድ የሰለጠኑ ነበሩ። በአባቶቻቸው የተማሩ፣ ወይም አስተማሪዎች ተቀጥሮላቸው እንዲማሩ የተደረጉ ነበሩ። ቤተሰቦቻቸውም ሀብታም ነበሩ። ከሀብታም ቤተሰብ በመወለዳቸው ግን አስተሳሰባቸው አልቀጨጨም። ለሰብአዊነት የቆሙና ዲስፖቲያዊ አገዛዝን የሚቃወሙና የሚታገሉ ነበሩ። አካሄዳቸው ግን ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ነበር። በእነሱ ዕምነትም ትክክለኛና ሁለገብ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በአመጽ ሳይሆን ሰፋና ጠለቅ ባለ ምርምርና ዕውቀት ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት ነው አገዛዞችና ፊዩዳላዊ አስተሳስብ የነበራቸውንና የሰውን ልጅ ኑሮ መሻሻል የማይፈልጉትን እንደ ካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችና ዕምነታቸውን መዋጋት የቻሉትና ህዝቦቻቸውም ከዘልማዳዊ የአኗኗር ሁኔታ እንዲላቀቁ መንገዱን ያመቻቹት። ወደኛ አገር ስንመጣ ግን ይህንን ዐይነቱን የዕውቀት ፍለግ ባለመከተላችንና፣ ሁኔታውም የሚያመችና የሚታወቅም ስላልነበር እስክንጎለምስ ድረስ ከሚሆነው ከማይሆነው ነገር ጋር በመተዋወቅ ሳናውቀው ጭንቅላታችን ውስጥ ብዙ ነገሮች ተሰግስገው በመግባት ራሳችንን ተገንዘብ የህብረተሰብአችንን የማቴሪያልና የስነ-ልቦና ሁኔታ በደንብ ልንረዳ አልቻልንም። ለመለወጥም የሚያስችል ፍቱን መሳሪያ ማዳበር አልተቻለም። ስለሆነም አብዮት ሲፈነዳ የኋላ ኋላ አለመደማመጥና  እንደዚያ ዐይነት አሰቃቂ ሁኔታ መፈጠሩ የሚያስገርም ጉዳይ አይደለም።

ስለሆነም በአገራችን ምድር በአብዮቱ ዘመን የነበረው የፖለቲካ ግንዛቤ ለህብረተሰብአዊ ለውጥ የሚደረገው ትግል ሰፋና ጠለቅ ያለ ውይይት(Political Discource) የሚያስፈልገውና ዲሞክራሲያዊ ግንዛቤን የሚጠይቅ መሆኑን ለተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ግልጽ ይሁን አይሁን የሚታወቅ ጉዳይ የለም። ማለት የሚቻለውና ሁኔታውም እንደሚያረጋግጠው በጊዜው የነበሩ የፖለቲካ ተዋናዮች ከግልጽ ውይይትና ጤናማ መተቻቸት ይልቅ አመጻዊ ትግልን የመረጡ ይመስሉ ነበሩ። አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በሙሉ ቀስና ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉ የሚያስመስላቸው ሳይሆን ስልጣን ለመያዝ ነበር። የአንድ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ማንነት የሚታወቀው በሚጽፈውና በድርጊቱ ስለሆነ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎችም ሊለኩ የሚችሉት በጊዜው  በነበራቸው ሚና ብቻ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የምንገነዘበው፣ ከፕላቶ ጀምሮ እስከካንትና እስከ ሄገል ያሉትን የፍልስፍና ምርምሮች አለፍ አለፍ ብለን ስናነብ አንድ ሰው ወይም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጭንቅላትን ለማዳበርና አንድን ነገር ሁለንታዊ በሆነ መልክ ለመገንዘብ የግዴታ ብዙ የዕድገትንና የግንዛቤ ደረጃዎችን ማለፍ እንዳለበት ነው። ሄገል ክስተታዊ የመንፈስ ሁኔታ(Phenomenology of the Spirit) በሚለው ስራው ውስጥ ይህንን  የማሰብ ወይንም የጭንቅላትን ዕድገት ሁኔታ ጉዳይና ፖለቲካዊ አስተሳሰብና በተግባር የሚመነዘሩ ድርጊቶች ከዚህ አንፃር መታየት እንዳለባቸው ነው የሚያሳስበው። በአገራችን ምድር ይህንን የመሰለው በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ምህራዊ እንቅስቃሴና የጭንቅላት መዳበር ሊታይ ባለመቻሉ የግዴታ እንደዚያ ያለ በቀላሉ ከታሪክ ሊፋቅ የማይችል ወንጀል ተሰራ።  ያም ተባለ ይህ ያለፈው አልፏል፤ ባለፈው ላይ ብንመላለስበት በሃዘን ከመሰቃየት በስተቀር ሌላ የምናተርፈው ነገር የለም። ማንኛውም አዲስ ትውልድ የትላንቱ ሁኔታ በአስተሳሰቡ ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ ቢያሳድርበትም መነሳት ያለበት ከዛሬው ሁኔታና ለመጭው ትውልድ ምን ዐይነት ታሪካዊ ስራዎች ልሰራ እችላለሁ? በማለት ነው። በተለይም ላይብኒዝ የሚባለው ታላቅ ሳይንቲስትና ሁለ-ገብ ምሁር ይህንን ነው የሚያሳስበን። የዛሬውንና የወደፊቱን ሁኔታ በመመልከት አፍጠው አግጠው በሚታዩ ችግሮች ላይ በመረባረብ የተረጋጋና የአማረ ህብረተሰብ ለመገንባት መጣር ነው ዋናው መመሪያ መሆን የአለበት።

ምን መደረግ አለበት !!

ከሃያ ስድስት ዓመት ጀምሮ በአገራችን ምድር ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ክስተት ተፈጥሯል። ወያኔ በመባል የሚታወቀው አገዛዝ ልክ ቀደም ብለው እንደተፈጠሩት ብሄራዊ አጀንዳ አለን እንደሚሉት ድርጅቶች ሁሉ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ የፈለቀ ነው። ከሌሎች ድርጅቶች የሚለየው የድርጅቱ አባሎች ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ ከተዘጋ ማህብረሰብ(Closed Society) የተፈጠሩና ጭንቅላትን በሚያድስ የመንፈስ ተሃድሶ ክንዋኔ ውስጥ ያለፉና የታነጹ ባለመሆናቸው በአስተሳሰባቸው የጠበቡና የራሳቸውንም ሁኔታ ከጠቅላላው የአገራችን ሁኔታ ጋር ማገናዘብ ያልቻሉና የማይችሉ ናቸው። በተጨማሪም ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በጋብቻ ያልተቀላቀሉ በመሆናቸው ሁሉንም የሚጠረጥሩና የሚጠሉም(ጠበቅ ብሎ ይነበብ) ነው የሚመስላቸው። ስለዚህም ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ነገር ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታዎች በመተርጎምና የራሳቸው የግል ሀብት አድርገው በመቁጠር ነው የህዝባችንን የመኖርና ያለመኖር ሁኔታ የሚደነግጉት። ለመኖርና ስልጣናቸውን ለማጠናከር ሲሉ በቀላሉ ሊገነዘቡ የማይችሉትን፣ ለጊዜውም ቢሆን ሀብት ለማካበት የጠቀማቸውን የኒዎ-ሊበራል ወይም የተቅዋም ማስተካከያ የኢኮኖሚ ዕቅድ ፖሊሲ(Structural Adjustment Program) ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰብአችንን አወቃቀርና የህሊና ሁኔታ ለማዘበራረቅ ችለዋል። ይህ ዐይነቱ ከሳይንስ ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለውና ለጠቅላላው ህዝብ ሀብት ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሌላው ኢ-ሳይንሳዊ ፖለቲካቸው ጋር ተደምሮ በአለፈው ወር እንዳየነውና ከመቶ ሰዎች በላይ የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ቆሻሻ አምራች በመሆን ጠቅላላው ፖለቲካቸው ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍና-አልባ መሆኑን አረጋግጧል። ይህ ዐይነቱ ፖለቲካዊ አመለካከትና ተግባራዊ የሆነውና የሚሆነው ፖሊሲ የተከታታይነትን መሰረተ-ሃሳብ የሚጥስ በመሆኑ  ህዝባችን ዘለዓለሙን እየተተራመሰ እንዲኖር የሚያደርግና፣ በህብረተሰቡ ውስጥም በተለያየ መልክ የሚገለጹ ውዝግቦችና ብልግና ፈጣሪዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ህዝቡ በፍርሃት እንዲኖር ተገዷል። አንዱ ሌላውን እንዳያምንና ትንሽ ጎልመስ ያለው ደካማውን ሊረዳ የማይፈልግበትና፣ በተለይም የወጣት ሴቶች መብት በከፍተኛ ደረጃ የሚጣስበት አገርና ማህበረሰብ ናት የዛሬይቱ ኢትዮጵያችን። በተጨማሪም በመንግስት የሚደገፉ ወይም መንግስት በስተጀርባቸው ያሉ የተደራጁ ቡድኖች ደካማውን እያስፈራሩ፣ ቤቱን እያፈራረሱበትና መሬቱን እየቀሙት ሜዳ ላይ እንደሚወረውሩት የሚሰሙትና የሚወጡት ዜናዎች ያረጋግጣሉ። ከዚህ ስንነሳ ዛሬ በአገራችን ምድር የሰፈነው አገዛዝ ዘራፊና  አሸባሪ እንዲሁም ፋሺሽታዊ  ነው ማለት ይቻላል።

ደጋግሜ ለማሳየት እንደሞከርኩት የዛሬው አገዛዝ ስልጣንን ለመጨበጥና ህዝባችንን ፍዳ ለማሳየት የቻለው ቀደም ብለው በነበሩ አገዛዞች በተሰራ ከሳይንስ ጋር በማይያያዝ ፓለቲካዊ ስህተት ነው። በተለይም ደግሞ በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረው ትርምስና አያሌ አሉታዊ ኃይሎች በመወለዳቸው ለእንደዚህ ዐይነቱ አገርን የሚያተራምስ ኃይል የፖለቲካ ክፍተት ሊፈጥሩ ችለዋል። ከዚህም በላይ ወያኔ የሚባለው ፍጡር ስልጣን ከጨበጠ በኋላ የአገራችንን ሁኔታ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ከመመርመርና ምሁራዊ የመታገያ መሳሪያ ከማዳበር ይልቅ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የራሱን ጨዋታ ነው መጫወት የጀመረው። ወደ ውስጥ ረጋ ባለና በሰፊ የምሁር መሰረት ላይ ተመርኩዞ አገዛዙን በሳይንስ ከመፈተንና ከመታገል ይልቅ እንዴት አድርጌ በአቋራጭ ስልጣን እይዛለሁ ወይንም እጋራለሁ በሚለው ላይ ነበር ሁሉም ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ያተኮረው። ስለሆነም አገዛዙ ከውጭ ኃይሎች ጋር ሆኖ በተለይም የእነሱን ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ አንድም ተቃዋሚ ኃይል የፖሊሲውን ምንነት በመረዳትና ትንተና በመስጠት ህዝባችንን ማስተማርና ማስረዳት አልቻለም። በዚህ መልክና ከመርጫ 1997 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሙሉ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሆነ ፖለቲካ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም በአለፉት 26 ዓመታት በፍልስፍና፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሶስይሎጂ፣ በህብረተሰብ ግንባታ፣ በከተማዎች ግንባታ፣ በአርክቴክቸርና በሌሎች ለህብረተሰብ ግንባታ በሚጠቅሙ መሰረታዊና አስፈላጊ ነገሮች ላይ ዳብሮ ሊወጣ የቻለ ፖለቲካዊ ኃይል የለም። ክርክርም ሲደረግ አይታይም። እንደቀደሙትና የዛሬው አገዛዝ፣ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውም ኃይል ፖለቲካ የሚባለውን መሰረታዊ ሃሳብ ላይ ከዘረዘርኳቸው ነገሮች ነጥሎ ነው የሚያየው። በዚህ መልክ የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዴት አድርጎ የህብረተሰብአችንን ችግር ሊፈታ ይችላል? እንዴትስ አድርጎ አገራችንን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊያደርጋት ይችላል? እንዴትስ የተከበረችና የጠነከረች ኢትዮጵያን ሊያስገነባ ይችላል ?

ይህ ዐይነቱ ፍልፍናና ሳይንሰ-አልባ ፖለቲካ እንደምናየው ብዙ የአፍሪካ አገሮችን እያተራመሰ ነው። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ህዝቦች የሀብታቸው ባለቤት መሆን ያልቻሉበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በመዋዕለ-ነዋይ(Direct Foreign Investment) ስም የውጭ ኩባንያዎች እየመጡና ከመንግስታቱ ጋር እየተመሰጣጠሩ የየአገሩ ህዝቦች መሬታቸውን እየተነጠቁና እንዲሰደዱ ሲገደዱ፣ በዚያውም መጠንም ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ውድመት እየደረሰና ማህበራዊ ቀውስም እየተፈጠረ ነው። አንዳንድ አገሮችና አካባቢዎች ደግሞ ወደ ጦር አውድማነት በመቀየር አንዳንድ መንግስታት የህዝቦቻቸውን ችግር ከመፍታትና አገራቸውን ከመገንባት ይልቅ ሽብርተኞችን መዋጋት አለባችሁ በሚል የየአገሮች የሰውና የተፈጥሮ-ሀብት እየባከነ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በሚቀጥለው ሁለትና ሶስት ትውልድ ላይ የራሱን ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያልፋል።

ከዚህ ስንነሳ የአገራችንም የፖለቲካ ትርምስ ይህንን የሚመስል ነው። ይሁንና ግን አብዛኛው ወይም ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በሙሉ ፖለቲካ ካልነው የዓለም ፖለቲካ አካሄድ ያልገባው ብቻ ሳይሆን የቱን ያህል ይህች ዓለም የሰይጣንነት ባህርይ በተናወጣቸው ጥቂትና ጊዜው በመጣላቸው ኃይሎች እንደምትሽከረከር ነው ሊረዳ የማይፈልገው። ይህንን እስካልተገነዘብንና ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአዲስ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ላይ መስርተን እስካላዋቀርነው ድረስ ህዝባችን የሚመኘውን ሰላምና ብልጽግና ልናመጣለትና የተከበረች ኢትዮጵያን መገንባት በፍጹም አንችልም።

ስለሆነም የወደፊቱ የፖለቲካ ሂደት በአዲስ ፍልስፍናና ሳይንስ ላይ መመስረቱ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ወጣት ኃይሎች ብቅ በማለት የፖለቲካ መድረኩን ከጎታች ኃይሎች መንጠቅ አለባቸው። በፖለቲካ እንቅስቃሴና በአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ማንኛውም አገር ሊያድግና ውስጣዊ ጥንካሬ ሊያገኝ የሚችለው የአንድ አገር ምሁር በራሱ ኃይልና ዕውቀት ሲተማመንና በአንዳች ዐይነት ፍልስፍና ሲመራና ሲደራጅ  ብቻ ነው። ለዚህ መሰረቱ ደግሞ የመንፈስ ተሃድሶና የባህል ለውጥ ያስፈልጋል። አብዛኛውን ዕውቀት የሚባሉ ነገሮች ልንፈጥራቸው የምንችላቸው አይደሉም። ተዘጋጅተው ያሉ ናቸው። ችግራችን ግን አብዛኛዎቻችን ምንጮችንና የአጠቃቀም ዘዴዎችን የምናውቅና እንዲገባንም የምንፈልግ አይደለንም። አብዛኛዎቻችን በተወሰነ „የአስተሳሰብ ክልል“(School of Thought) የሰለጠን ስለሆን ከዚህ በፍጹም ለመላቀቅ አንፈልግም። ይህንን እንደ ዕምነት ወይም እንደ ርዕዮተ-ዓለም የሙጥኝ ብለን በመያዝ ራሳቸን ተሰቃይተን ህዝባችንን እናሰቃያለን። በመሰረቱ ነገሩ ቀላል ነው። ጥይቄዎችን መጠየቅ ነው። ለምን አውስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ወይም ሌሎች አደጉ የሚባሉና የምንኖርባቸው አገሮች እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ እኛንስ ምን ተሳነን ? ስህተቱስ ከምን ላይ ነው? ብሎ መጠየቅ ብቻ ነው። እንደዚህ ዐይነቱን ጥያቄ የምናቀርበው ዋናው ህልማችንና አላማችን ከታወቁ ብቻ ነው። የለም ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስፈልጋቸው የድሮው ዐይነት አገዛዝ ነው፤ ስለዚህም በውጭ ኃይሎች እየታሸን መኖር ነው የምንፈልገው የምንል ከሆነ ብዙም የሚያከራክረን ነገር የለም። በሌላ ወገን ግን ወደ ኋላ ተመልሰን የድሮውን ስርዓት ነው መመስረት የምንፈልገው ብንል የሚቻል አይደለም። የኛ ችግር ወደ ኋላ ለመመለስ የማንችለውን ያህል ወደፊት እንዴት እንደምንሄድና አዲስ ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ መመስረት ያለመቻሉ ላይ ነው። በዚህ መልክ ግራ በመጋባታችን የተነሳ ያለን አማራጭ ሁሉም በየፊናው ተደራጀሁ እያለና የብሄረሰብ ፈሊጥ የሚባለውን ነገር እያራገበ በሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ ግራ እያጋባ ነው።

ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት የፖለቲካ ድርጅቶችና የአክቲቪስቶች ቁጥር መቀነስ አለበት። በሁለተኛ ደረጃ ለፖለቲካ ነፃነት የሚታገል ግለሰብም ሆነ ድርጅት የተወሰኑ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት አለበት። በሶስተኛ ደረጃ፣ የግዴታ የፓራዳይም ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። በአራተኛ ደረጃ፣ ለስልጣን የሚደረገውን እሽቅድምድሞሽ መተውና ሁሉም በተማረው ትምህርት ዙሪያ ሰፊ ምርምር በማድረግ ጥናታዊና ወደ ተግባር ሊመነዘሩ የሚችሉ ጽሁፎችን ማውጣት መቻል አለበት። ለምሳሌ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ወይንም ኢንጂነሪንግ የተማረ ሰው የተማረውን ትምህርት እርግፍ አድርጎ ባላደገበትና ባልሰለጠነበት ሙያ ውስጥ በመግባት ለምንድን ነው ፖለቲከኛ ነኝ እያለ ሰውን ግራ የሚያጋባው? አንድ ሰው በፊልዱ ቢመራመርና ለህብረተሰብአችን የሚጠቅሙ ነገሮችን ቢያበረክት ይህ በራሱ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ የፖለቲካ አስተዋፅዖ ነው። ለምሳሌ በባዮሎጂ ወይም በፊዚክስ የሰለጠኑ ምሁራን ብዙ ነገሮችን መስራት ይችላሉ። ባዮሎጂስቱ እንደሰለጠነበት የሙያ ዘርፍ፣ ለምሳሌ በፕላንት ሳይንስ የሰለጠነ ኢትዮጵያን እንደገና ወደገነትነት ሊለውጣት ይችላል። ወደ በረሃማነት የተለወጡ አካባቢዎችን ሊያለማቸው ይችላል። የጥንትና የወደሙ ዛፎችን እየፈላለገ እንደገና ሊያረባቸውና ለብዙ አካባቢዎች አዲስ ህይወት ሊፈጥር ይችላል። እንደዚሁም በፊዚክስ ሙያ የሰለጠነ ምሁር አዳዲስ መሳሪያዎችን ሊፈጥር ይችላል። እንደሚታወቀው ዛሬ የምንጠቅምባቸው ቴክኖሎጂዎች በሙሉ የፊዚክስ ምርምር ውጤቶች ናቸው። አንድ አገርም ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት ልታፈራና ተከታታይነት ያለው ቴክኖሎጂ ልታዳብር የምትችለው በፊዚክስ አማካይነት ብቻ ነው። ከፊዚክስ ውጭ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊኖር በፍጹም አይችልም። ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ኃይልና ፋይን ሜካኒክስ የሚባሉ ነገሮች በሙሉ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረቶች ሲሆኑ፣ መሰረታችውም ፊዚክስ ነው። ስለሆነም በፊዚክስ ላይ ርብርቦሽ ካልተደረገ ወደፊት መራመድ አንችልም። ዛሬ በአገራችን ምድር የሚታየው መዝረክረክነትና ቆሻሻዎችን በየቦታው መጣል፣ ውሃን ከመሬት አውጥቶ በየቤቱ ማዳረስ አለመቻል፣ ፍሳሽን በስነ-ስርዓት እንዲጸዳና እንደገና ለመታጠቢያና ለምግብ መቀቀያ ለማድረግ ያለመቻል፣ ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው የቱን ያህል ሳይንስ፣ በተለይም ፊዚክስ በአገራችን ምድር ያልተስፋፋ መሆኑን ነው። ከዚህ ስንነሳ ሁሉም በሰለጠነበት ሙያ አስተዋጽዖ ለማድረግ ቢጥር ፖለቲካ ላይ ከተቀመጡ ሰዎች የተሻለ ህዝባዊ ተቀባይነት ይኖረዋል፤ በታሪክም ሲታወስ ይኖራል።

በአንደኛና በሁለት ደረጃ የጠቀስኳቸውን መሰረተ-ሃሳቦች መቋጠሪያ ለማሲያዝ፣ በፖለቲካ ስም እዚህና እዚያ እንቀሳቀሳለን የሚሉ ድርጅቶች እንደ ዕውነቱ ከሆነ በደንብ የተዋቀሩና በስራ-ክፍፍል ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ነን ባዮች መሪዎቻቸው ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በላይ በመሪነት የተቀመጡባቸው ሲሆኑ አዲስ አስተሳሰብ ሲያፈልቁ አይታዩም። አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ወይም ፓርቲዎች ወደ ግልሀብትነት የተለወጡና በውስጣቸውም ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ መንሸራሸር የሚታይባቸው አይደሉም። ከበተቻ ያሉ አባሎች ደግሞ መሪዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ስህተት ቢሰሩ እንኳ የሚጋፈጧቸውና የራሳቸውን አስተሳሰብ ለማስፋፋትና አማራጭ ሊሰጡ የሚችሉ አይደሉም። በተጨማሪም አንድም የፖለቲካ ድርጅት የጥናት መጽሄትም ሆነ ጋዜጣ አያወጣም። አንድ ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ የሚያሰኘው ርዕዩን የሚያስፋፋበት በየወሩ የሚታተም ጋዜጣና፣ በየሶስት ወሩ የሚወጣ መጽሄት ሲኖረው ብቻ ነው። ፕሮፌሰር ደጀኔ በቃለ-ምልልሳቸው በሚገባ እንዳብራሩት ፓርቲዎች ሃሳብ የሚንሸራሸርባቸውና  አማራጭ ሃሳብም ለውድድር የሚቅርቡባቸው መድረኮች  መሆን አለባቸው። ይህ በሌለበት ቦታ አንድ ድርጅት ፓርቲ ነኝ ብሎ ራሱን መጥራት አይችልም። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ ፊዩዳላዊ አሰራር መላቀቅና፣ ዘመናዊና የተሻለ አሰራር ጋር መለማመድና መማር ያስፈልጋል። በተለይም መሪዎች አመራርን ለመስጠትና ሃሳብን ለማፍለቅ የሚችሉ እንጂ እንደጌታ መታየት የሚፈልጉ መሆን የለባቸውም። በአብዛኛዎቹ ፓርቲ ነን በሚሉ ድርጅቶች ውስጥ ያለው ያሰራር ሁኔታ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በፊዩዳሏ ኢትዮጵያ ዘመን በአባቶቻችንና በእናቶቻችን፣ በባልና በሚስት መሀከል የነበረውን ዐይነት ግኑኝነት ነው የሚመስለው። መሪ ነኝ የሚል ልዩ መስተናግዶ የሚፈልግና ማንም አፉን አውጥቶ ሊጠይቀው አይችልም። ሲመጣ የፈለገውን ተናግሮና ተጨብጭቦለት ማንም ሳይጠይቀውና ሳያፋጥጠው ተጋብዞ ወደ መጣበት ተመልሶ ይሄዳል። ጋባዢዎች ራሳቸውም በቂ የፖለቲካ ዕውቀት ስለሌላቸው የሚጋብዙትን ሰው እንደ ልዩ ፍጡር ነው የሚመለከቱት። ይህ ዐይነቱ የአሰራርና የአመላካከት ሁኔታ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን በሃይ-ቴክ ደረጃ በምንገኝበት ወቅት መታየት የሌለበት ነገር ነው። እንደኛ ለመሳሰለው በአውሮፓ የምሁር እንቅስቃሴና በካፒታሊዝም ውስጥ ላደግነውና ሶሻላይዝድ ለሆንነው እንደዚህ ዐይነቱ ፊዩዳላዊ አሰራርና አካሄድ የሚዋጥልን አይደለም። ለምርምር፣ ለጥያቄና ለፈጠራ የሚያመች አይደለም። በአንድ ፓርቲ ውስጥ የአሰራር ሂራርኪ ቢኖርም፣ በአባሎቹ መሀከል የመፈራራት መንፈስ ማደር የለበትም፤ በጓደኛምነትና በመከባበር ደረጃ ብቻ ነው መተያየት ያለባቸው። በተጨማሪም እያንዳንዱ ለህሊናውና ለዕምነቱ መገዛት አለበት። ስለሆነም መሪዎች እንደአዋቂ በመቅረብ ከበታች ያሉትን ማስፈራራት የለባቸውም። በተጨማሪም ለመሪዎች የጊዜ ገደብ መሰጠት አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ መሪ ነኝ የሚል ከውጭ ኃይሎች ጋር ግኑኝነት ከመፍጠሩና ለማነጋገር ቀጠሮ ከመውሰዱ በፊት፣ ወይም የአቤቱታ ደብዳቤ ከመጻፉ በፊት የግዴታ በውስጥ ሰፋ ያለ ውይይት ማደረግ ያስፈልጋል። አንድ መሪና የአመራር አካል የፓርቲው ደንብ ውስጥ ከሰፈረው መሰረተ-ሃሳብ ውጭ እንደፈለገው የመንቀሳቀስ ዕድል ማግኘት የለበትም። ማንኛውም ፓርቲ አንድ ቀን አገሩን ስለሚወክልና የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል የሚወስን በመሆኑ፣ ማንኛውም ፓርቲ ከመጀመሪያውኑ በጥራት ከታች ወደ ላይ በሃሳብ ዙሪያ መደራጀት አለበት። ዲሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበርና የፓርቲ አውቃቀርን ባህል መማር አለበት። ፓርቲዎች የስልጣን መወጣጫ መድረኮች ሳይሆኑ የዕውቀት መድረኮች መሆናቸውን ማንኛውም እንዲገነዘበው ያስፈልጋል። ስለሆነም በየጊዜው ሁሉም በሚችለው መስክ በመሰማራትና በማጥናት ጥናቱን ለውይይት ማቅረብ አለበት።

ሌላውና አስቸጋሪው ነገር አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅት ነን ባዮች በውስጣቸው የስራ-ክፍፍልና በተለያየ የሙያ መስክ የሰለጠኑ ምሁራን የሏቸውም። ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በፖለቲካ፣ በህግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በከተማ ዕቅድና በቤት አሰራር፣ በኢኮኖሚና በፋይናንስ፣ በፍልስፍናና በሶስዮሎጂ፣ በሳይኮሎጂ፣ በጤና ጥበቃ፣ እንዲሁም በሴቶችና በወጣቶች ጥያቄ ላይ የሰለጠኑ ሙያተኞች ያስፈልጉታል። ይህ ዐይነቱ አደረጃጀት ወደፊት አንድ ነገር በሚከሰት ጊዜ ስልጣንን ለመረከብ ያመቻል። ስልጣንን የሚረከበውም ሆነ የሚነጥቀው ድርጅት ቀድሞውኑ የተዘጋጁ ሙያተኞች ስላሉት የአገርን ጉዳይ በሚመለከት ቶሎ ቶሎ ብሎ መስመር ለማስያዝ ያመቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ርዕይ ወይም ርዕዮተ-ዓለም እንዲኖረው ያስፈልገዋል። ለዲሞክራሲና ለነፃነት ነው የምንታገለው የሚለው አጠቃላይ አነጋገር ብዙም የሚያስኬድና ችግርንም ለመፍታት የሚያመች አይደለም። ከዚህ ስንነሳ እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደሚታገልና የሚፈልገውንም እንዴት እንደሚያዋቅር በደንብ ማስረዳት አለበት። የገበያ ኢኮኖሚ መገንባትና ሊበራል የሆነ ህብረተሰብ ነው የምንፈልገው የሚለው በራሳቸው ላለንበት የተወሳሰቡ ችግሮች እንደመፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም። በራሳቸውም ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት ሊሆኑ አይችሉም። ስለሆነም እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ለሶሻሊዝም፣ ለካፒታሊዝም ወይም ለፊዩዳሊዝም የሚታገል መሆኑን ቢነግረን ካለንበት ውዥንብር ልንላቀቅ እንችላለን።  ይህ ግልጽ እስካልሆነ ድረስ እዚህና እዚያ የሚደረገው ሩጫ የትም የሚያደርሰን አይደለም። የሃሳብና የአመለካከት ጥራትም እንዲኖረን አያደርገንም።

ከዚህ ስነሳ የምገነዘበው ነገር አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደሚታገሉ የሚያውቁ አይመስለኝም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ የሶስት ሺህ ዐመታት ታሪክ አለው የሚባል አገር በዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ላይ ግልጽ አመለካከትን ይጠይቃል። እንደሚታወቀው አገራችን ላለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰብአዊ፣ የስነ-ልቦናና የባህል ችግር፣ እንዲሁም የፖለቲካና የርዕይ ችግር የብሄረሰብ መብትን በማወቅ የሚፈታ ነገር አይደለም። የአገራችን ችግሮች ፖለቲካዊ፣ መንግስታዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የአካባቢ መውደም ወይም መቆሸሽ ጉዳይና፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጥያቄዎች እንደመሆናቸው መጠን ጠቅላላውን፣ በዛች ምድር የሚኖረውን ህዝብ የሚመለከቱ ናቸው። ይህም ማለት ያሉት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት፣ በፍልስፍና፣ በሶስዮሎጂ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር አፍጠው አግጠው የሚታዩት ችግሮች፣ ማለትም የከተማዎች በስነ-ስርዓት አለመገንባትና ህዝባችንም ባልባሌ ቦታዎች እየተሰቃየ መኖር፣ የሚጠጣው፣ የሚቀቅልበትና የሚታጠብበት ንጹህ ውሃ አለማግኘት፣ አስፈላጊው ለሰውነት ገንቢ የሆኑ የተለያዩ የምግብ ዐይነቶችን በብዛትም ሆነ በጥራት አለማግኘት፣ ለማሞቂያ፣ ለመቀቀያና ለመብራት የሚያገለግል የኃይል ጉዳይ፣ የህክምናና የትምህርት ጉዳይ፣ ለወጣቱ የሙያ ማሰልጠኛ ቦታ አለማግኘት፣ በየቦታው የስራ መስክ የሚከፍቱ ትናንሽና ማዕከለኛ እንዱስትሪዎች አለመኖር… ወዘተ. እነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ ህብረተሰብአዊ እንደመሆናቸው መጠን የብሄረሰብን መብት በማወቅ የሚፈቱ ሳይሆኑ፣ በጠለቀና ተከታታይነት ባለው የሳይንስ ምርምር ብቻ ነው። ስለሆነም ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በዚህ መሰረታዊ ጥያቄና በአፈታቱ ላይ ግልጽ አመለካከት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ለምን ዐይነት ህብረተሰብ ነው የምንታገለው? የሚለውን ለመመለስ የሚከብድ አይመስለኝም። ወደድንም ጠላንም ማንኛውም ህብረተሰብ አጠቃላይና ሁሉንም ሊያሰባስብ የሚችል ርዕይ ያስፈልገዋል። ሊያሰራ የሚችል፣ ኃይልን የሚሰበስብና በአገር ውስጥ ያለን የተፈጥሮ ሀብት በስነስርዓት አውጥተን በቴክኖሎጂ አማካይነት ለመለወጥና የህዝባችንን ፍላጎቶች ለመመለስ የምንችለው አንዳች ዐይነት ርዕይ ሲኖረን ብቻ ነው። ይህ ማለት ግን ሁላችንም አንድ ዐይነት አመለካከት ይኑረን ማለቴ አይደለም፤ ሊኖርም አይችልም። ለማለት የምፈልገው በዚህ ላይ ግልጽ አመለካከት ካለን ያሉንን ችግሮች መረዳትና መልስም ለመፈለግ ይቀለናል።

በአጭሩ በፖለቲካው መስክ የሚሳተፉና እንሳተፋለን የሚሉ ግለሰቦችና ድርጅትም ለመመስረት የሚፈልጉ ሁሉ በመጀመሪያ ደረጃ ከላይ እንዳልኩት የረጅም ጊዜ የቲዎሪ፣ የሳይንስና የፍልስፋና ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም በየጊዜው በተከታታይ ህብረተሰብአችንን የሚመለከቱ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ማቅረብ አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻና፣ ፖለቲካ የሚባለውን ነገር በደንብ የተገነዘቡ ከሆነና ለማስተማርም የሚችሉ ከሆነ በእርግጥም ኃላፊነትን ሊሸከሙ ይችላሉ። ስለሆነም የመጀመሪያው እርምጃ ሰፋ ባለና ሁለ-ገብ በሆነ የምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ሲሆን፣ በዚህ መሰረት ብዙ ነገሮችን ማቃለል ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ ክርክርና መቻቻልን በመማር ለሰፊው ህዝብ አዲስ ህይወት መለገስ ይቻላል። አንድ አትክልት ለማደግና ፍሬ ለመስጠት ውሃና ሚኒራሎች እንደሚያስፈልጉት ሁሉ ለአንድ ፓርቲ ማበብና ውስጣዊ ጥንካሬ ማግኘት ዲሞክራሲያዊ ክርክርና ውይይት እጅግ አስፈላጊ ናቸው ።

የዛሬውን  የወያኔን አገዛዝ በሚመለከት አገዛዙ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ሊጂቲሚሲ የሌለው በመሆኑ ከሱ ጋር የሚደረገው „ድርድር“ ሁሉ ጊዜ ማባከኛና የእሱን ዕድሜ ማራዘሚያ ብቻ ሳይሆን፣ አዳዲስ ሁኔታዎችን እየፈጠረ የአገራችንን ሁኔታና ትግሉን ውስብስብ እንዲያደርግ የሚያመቻች ነው። በአገር ቤት ውስጥ ያሉ „ተቃዋሚ“ ነን የሚሉ፣ በመሰረቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልሆኑና በደንብ ያልተደራጁ ድርጅቶች ከአገዛዙ ጋር „ድርድር“ ሲያደርጉ በአገር ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታ የሚታያቸው አይመስልም። አገዛዙ እንደዚያ ሰው እየጨፈጨፈ፣ እያቃጠለና በመርዝ እየገደለ፣ ሌሎችም ለጭንቅላት የሚዘገንኑ ነገሮችን እየሰራ ምን ለማምጣት ነው ከእንደዚህ ዐይነቱ መንፈሱ እንዳለ ከተሟጠጠ አገዛዝ ጋር „መደራደር“ የሚቻለው? ከእንግዲህስ ወዲያ የገዢው አባላት ሰዎችን አስተሳሰብ በመቀየር ሰብአዊ እንዲሆኑና ሁለ-ገብ በሆነ የአገር ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ ይቻላል ወይ? በእኔ ዕምነት ይህ ዐይነቱ አካሄድ በመቶ ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመጭው ተከታታ ትውልድና ታሪክ ላይ መቀለድ ይመስለኛል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው የውስጥ ኃይል „ድርድር“ ሲያደርግ በእርግጥስ በአገራችን ምድር በዚህ አማካይነት መሰረታዊ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል ብሎ ያምናል ወይ?  እንደሚገባኝ ከሆነ እነዚህ የውስጥ ኃይሎች በኢትዮጵያ ምድርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የገባቸውና የሚታያቸውም አይመስለኝም። አካሄዳቸው በሙሉ በዚህም በዚያም ብለው የስልጣን ተካፋይ ለመሆን ከመፈለግ በስተቀር በተሻለ ርዕይ ለመታገልና በአገር ግንባታ ውስጥ ለመሳተፍ የሚችሉ አይደሉም። የእኔም መልዕክት እነዚህ በደንብ ያልተደራጁ ድርጅት ነን ባዮች „መደራደራቸውን“ ማቆም ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ዓለምም መገለል ያለባቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                              ፈቃዱ በቀለ

                                                                        fekadubekele@gmx.de

 ለማነፃፀርና ለማገናዘብ እንዲያመች ከታች የተዘረዘሩትን መጽሃፎች ተመልከቱ። ለአገር ዕድገት ሊጠቅሙ የሚችሉ መጽሀፎች ናቸው !!

Philosophical  and Political Books

  1. Albrecht Dihle, The Theory of Will in Classical Antiquity, Los Angeles & London, 1982
  2. Alexander S. Kohanski, The Greek Mode of Thought in Western Pilosophy, London & Toronto, 1984
  3. Allen W. Wood(ed.), Hegel, Elements of the Philosophy of Right, Cambridge, UK, 2003
  4. Amit Goswami, How Quantum Activisim Can Save Civilization: A Few People Can Change Human Evolution, US, 2011
  5. Bob Jessop, The Capitalist State, Oxford, 1982
  6. Eric Voegelin, The New Science of Politics: An Introduction, London & Chicago, 1987
  7. Francis Hutcheson, An Inquiry into the Original of Our Ideas of Beauty and Virtue, New York, 1971
  8. Georg di Giovanni(translated), George Wilhelm Friedrich Hegel, The Science of Logic, Cambridge, UK, 2010
  9. Georgi Stankow, The Universal Law through the Mirror of Philosophy, Stankow’s Universal Law Press, 1999
  10. Georg Wilhelm Friedrich Hegel, The Phenomenology of Spirit, Oxford Uiniversity Press, 1977
  11. John E. Atwell, Schoppenhauer on the Character of the World: The Metaphysics of Will, Los Angeles, 1995
  12. John Stuart Mill, On Liberity, Batoche Books, Ontario, 2001
  13. Nicholas Rescher, Process Metaphysics: An Introduction to Process Philosophy, New York, 1996
  14. Nicos Poulantzas, The Theory of State: Political Superstructure, Ideology and Democratic Socialism, Hamburg, 1978
  15. Paul Wilpert(ed.), Nicholas Of Cusa: On Learned Ignorance, US, 1985
  16. Raphael Demos(ed.), Plato Selections, New York, 1955
  17. Robert C. Trundle,Jr, Ancient Greek Philosophy: It’s Development and Relevance to OurTime, USA, 1994
  18. Stjepan G. Meštrovic, The barbarian temperament: Toward a postmodern critical theory, London & New York, 1993
  19. K.Seung, Plato Rediscovered: Human Value and Social Order, London, 1996
  20. K.Seung, Kant’s Platonic Revolution in Moral and Political Philosophy, Baltimore & London, 1994

Scientific Books

  1. Diogenes Allen, Mechanical Explanations and the Ultimate Origin of the Universe according to Leibniz, Wiesbaden, 1983
  2. Donald M.Davis, The Nature and Power of Mathematics, UK, 1993
  3. James Barry Jr., Measures of Science: Theological and Technological Impulses in Early Modern Thought, Illinois, 1996
  4. Karl Popper, The Logic of Scientific Discovery, London& New York, 1992
  5. Karl Popper, The Open Society and its Enemies, London & New York, 2002
  6. Ludwig Edelstein, The Idea of Progress in Classical Antiquity, Baltimore & Maryland, 1967
  7. Margaret Jacob, Scientific Culture and the Making of the Industrial West, New York, 1997
  8. Morris Kline, Mathematics and the Search of Knowledge, New York & London, 1985
  9. Rupert Sheldrake, The Science Delusion, London, 2013

 

 

Economics Books

 

  1. Adolph Lowe, Essays in Political Economics, New York & Frankfurt am Main, 1987
  2. Birger P. Priddat, The Other Economy, Marburg, 1995
  3. Catherine Cowley, The Value of Money, London & New York, 2006
  4. Clive Trebilcock, The Industrialization of the Continental Powers: 1780-1914, New York, 1981
  5. Cristiano Antonelli, The Economics of Innovation, New Technologies & Structural Change, London & New York, 2003
  6. David Orrell, Econo Myths: Ten Ways That Economics Gets it Wrong, London, 2010
  7. David S. Landes, The Wealth and Poverty of Nations, New York & London, 1999
  8. David Landes, The Unbounded Prometheus: Technolgical Change and Industrial Development in Western Europe from 1750 to the present, Cambridge, UK, 2003
  9. Doug Bandow & Ian Vásquez(eds.) Perpetuating Poverty. The World Bank, the IMF, and the Developing World, US, 1994
  10. Eric Dorn Brose, The Politics of Technological Change in Prussia: Out of the Shadow of Antiquity, 1809-1848, New Jersey 1993
  11. Erik S.Reinert, How Rich Countries Got Rich… and Why Poor Countries Stay Poor, London, 2007
  12. A. Brett, International Money and Capitalist Crisis: The Anatomy of Global Disintegration, Colorado, 1983
  13. Esben Sloth Anderson, Evolutionary Economics, London & New York, 1994
  14. Friedrich Engels(ed), Karl Marx, Capital(Vol I, II & III): A Critical Analysis of Capitalist Production, New York, 1975
  15. Fredrick G. Lawrence(ed.), Collected Works of Bernard Lonergan, Macroeconomic Dynamics: An Essay in Circulation Analysis, London, 1999
  16. Fredrick Soddy, Wealth, Virtual Wealth & Debt: The Solution of the Economic Paradox, London, 1983
  17. Gary Herrigel, Industrial Constructions: The sources of German industrial power, New York, 1996
  18. Geoffrey M. Hodgson, Economics and Evolution, Cambridge, UK, 1993
  19. Geoffrey Hodgson, The Evolution of Institutional Economics, Routledge, London, 2004
  20. Heinrich Pesch, Teaching Guide to National Economics, Freiburg, 1923
  21. James Angresano, The Political Economy of Gunnar Myrdal, Cheltenham, UK, 1997
  22. Joseph A. Schumpeter, The Theory of Economic Development, Cambridge & Massachusetts, 1951
  23. Lyn Marcus, Dialectical Economics. An Introduction to Marxist Political Economy, Massachusetts, Toronoto & London, 1975
  24. Makato Itoh, The Basic Theory of Capitalism: The Forms and Substance of the Capitalist Economy, Hong Kong, 1988
  25. Maxine, Berg, The Machinery Question and the Making of Political Economy, London & New York, 1980
  26. Michel Aglietta, A Theory of Capitalist Regulation. The US Experience, London, 1979
  27. Neil de marchi(ed.), Non-Natural Science: Reflection on the Enterprise of More Heat than Light, Drham & London, 1993
  28. Nicholas Georgescu-Roegen, Analytical Economics, Cambridge & Massachusetts, 1966
  29. Orio Giarini, Dialogue on Wealth and Welfare. An Alternative View of World Capital Formation, New York & Toronto, 1980
  30. Paul Mason, Postcapitalism: A Guide to our Future, UK, 2016
  31. Paul Mattic, Marx and Keynes,Wien, 1969
  32. Richard Arena & Cécile Dangel-Hagnauer(eds.), The Contribution of Joseph Schumpeter to Economis. Economic Development and Institutional Change, London & New York, 2002
  33. Richard A. Goldthwaite, The Economy of Renaissance Florence, Balitmore & Maryland, 2009
  34. Rod Hill & Tony Myatt, The Economics Anti-Textbook: A Critical Thinker’s Guide to Micro-Economics, London & New York, 2010
  35. Steve Keen, Debunking Economics, London & New York, 20111
  36. Stuart Corbridge, Capitalist World Development. A Critic of Radical Development Geography, US, 1986
  37. Tom Burgis, The Looting Machine, War Lords, Tycoons, Smugglers and the Systematic Theft of Africa’s Wealth, London, 2016
  38. Vivian Walsh & Harvey Gram, Classical and Neoclassical Theories of General Equilibrium, New York 1980
  39. Wangari Maathai, The Challenge for Africa, UK, 2009

 

Links

FORUM – Inforadio
Drama oder Chance –
Folgen des Ukraine-Kriegs für Afrika


(Bild: rbb/Matthias Schirmer)

Beitrag: Audiodatei

Weitere Links:

Books

African Predicaments & the Method of solving them effectively

 

(English) Book – 30. August 2016


 

Deutsch – Amharisch / Amharisch – Deutsch

von Fekadu Bekele und Bosena Negussie | 25. Januar 2019

 

 

Capitalism

Fekadu Bekele

 


Fekadu Bekele

Gesellschaftsformation und Artikulation von Produktionsweisen in Äthiopien