[gtranslate]

 

አሜሪካን ሲያስነጥሰው ጠቅላላው ዓለም ማልቀስ ጀመረ !!

የሰሞኑን ፊናንስ ቀውስና የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት

                                                                                                                                                                                                                                                             ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                                                 ግንቦት 10፣ 2008

መግቢያ

 

          አንድ በጀርመን የሚታተም „ The New Solidarity „ የሚባል ጋዜጣ በ 06.09.2006 ዓ.ም ባወጣው እትሙ በመጀመሪያው ገጽ ላይ፣ „ አሜሪካ በብድር የተሰሩ ቤቶች ወደ መንኮታኮት ላይ ናቸው“  ብሎ ሰፋ ያለ ትንተና በመስጠት፣ በአንድ የኢኮኖሚ መስክ የተከሰተው ቀውስ የዓለምን የፋይናንስ ገበያ እንደሚያናጋው ተንብይቶ ነበር። በዚህ መልክ፣ ሜይን ስትሪት አመለካከት ከሌላቸው ጋዜጦችም ሆነ መጽሄቶች የወጡትና የሚወጡት እትሞች፣ እ.አ. ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ልቅ እየሆነ የመጣውን የፋይናንስ ገበያ መንግስታዊ ቁጥጥር ካልተደረገበት ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል አጥብቀው አሳስበው ነበር። በተለይም በየሰከንዱና በየደቂቃው ትርፍ ለማካባት ሲባል በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጹ የፋይናንስ ምርቶችን( Financial Products) ወዲህና ወዲያ ማሽከርከር የመጨረሻ መጨረሻ በቀላሉ ሊቆም የማይችል ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ቀውስ እደሚያመጣ በሰፊው እየተነተኑ ለማስረዳት ሞክረዋል። ማንም የሰማቸው አልነበረም። እንዲያውም ይህ የእብዶች ቅጀት ነው እየተባለና፣ ቀውስ ሊከሰት ቢችል እንኳ፣ የገበያ ኢኮኖሚ በራሱ የውስጥ ኃይል ራሱን ማረም እንደሚችልና በተለያዩ የገበያ መስኮች ዘንድ ሚዛናዊ ሁኔታ እንደሚፈጠር ይምሉ ይገዘቱ ነበር። በተለይም፣ በጊዜው የአሜሪካን ፊዴራል ባንክ ዋና ኃላፊ በነበሩት፣ በሚስተር አላን ግሪን ስፓን የሚሰጠው ምክንያት፣ ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ ብቃትነት ያለውና ራሱን በራሱ ማረም ስለሚችል ቀውስ በፍጹም ሊከሰት አይችልም የሚል ነበር። ሰሞኑን በአሜሪካን ኮንግረስ ፊት ቀርበው ስለአሁኑ የፋይናንስ ቀውስ ገለጻ ያደረጉት ሚስተር አላን ግሪን ስፓን፣ እንደዚህ ከቁጥጥር የወጣ ቀውስ ይከሰታል ብለው እንዳልጠበቁ ተናግረዋል።

         ሰሞኑን በዜና ማሰራጫዎች አንደሚወራው፣ የፋይናንስ ገበያው ቀውስ እንደክፉ የወረርሽኝ በሽታ፣ የካፒታሊስት ሃገሮችን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ከዚህ የፋይናንስ ገበያ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተቆላለፉትን ሃገሮችንም እያናጋ ነው። የአክስዮን ገበያ( Stock Market) ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጣም ከፍና ዝቅ በማለት ጠቅላላውን ገበያ እያተራመሰው ነው። ስለሆነም ከአማሪካ እስከ ጃፓን፣ ከጃፓን እስከ ቻይናና ሌሎችንም የአሺያ ሃገሮች በመምታትና፣ ወደ ጀርመንና ወደ ሞስኮ በመዳረስ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው። በተለይም የፋይናንስ ገበያው ቀውስ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚው መስክም(Real Economy) ሊሸጋገር ይችላል- ባሁኑ ወቅት የተጨባጩን ኢኮኖሚም እየመታው ነው- በሚል ጭምጭምታ መደናገጥን አስከትሏል። በመሆኑም፣ ሰፋ ያለ ገበያ ያለው አሜሪካ ከውጭ የሚያስገባቸውን  እንደመኪናና ሌሎችንም እቃዎች በመቀነሱ፣ በተለይም እንደ ጃፓንና ጀርመን የመሳሰሉ በአሜሪካ ገበያ የሚመኩ ሃገሮች ምርታቸውን በመቀነስ ሠራተኞችን ለጊዜውም ቢሆን ወደ ማባረር ደርሰዋል፤ የተቀሩትን ደግሞ የተወሰኑ ሰዓቶች ብቻ እንዲሰሩ በማድረግ ላይ ናቸው። በአሜሪካ ገበያ ላይ የምትመካው ቻይናም የቀውሱ ቀማሽ በመሆን፣ ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢዋ እየቀነሰ በመምጣት ላይ ነው። በመሆኑም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚው እየተዛመተ የመጣው የፋይናንስ ገበያ ቀውስ አስር ዓመት ያህል እየጦፈ የመጣውን የጥሬ ሀብት ዋጋ፣ በተለይም የዘይትን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ እንዲል እያደረገው ነው። ከስድስት ወር በፊት አንድ በርሜል ዘይት በአሜሪካን ዶላር ሲተመን እስከ መቶ ሃምሳና ከዚያም በላይ ያልተተኮሰውን ያህል ፣ በአሁኑ ወቅት በመቶ ፐርሰንትና ከዚያም በላይ ዝቅ በማለት የጥሬ ሀበቱን ገበያ እያናጋው ነው። የዘይት ዋጋ በአሁኑ ወቅት ወደ 70 የአሜሪካ ዶላርና ከዚያም በታች መቀነስ ለተጠቃሚው ጥሩ የሆነውን ያህል፣ በዘይት ሽያጭ ገቢ የሚመኩ በተለይም እንደ ራሺያና ቬኔዙዌላ የመሳሰሉ ሃገሮች የባጀታቸው ሁኔታ አስተማማኝ ወዳለመሆን እየመጣና፣ ያቀዱትንም ፕሮጀክቶች ሊያቀዘቅዙ ወይም ሊያቆሙ የሚችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።

          ከዚህ በመነሳት የፋይናንስ ገበያውን ሁኔታ ረገብ ለማድረግና በኢንቬስተሮች መሀከል መተማመን እንዲፈጠር ወለድን የመቀነስ ወይም የከሰሩ ባንኮችን፣ በተለይም የኢንቬስትሜንት ባንኮችን ለማዳን የተወሰዱት እርምጃዎች( Bail Out) በሙሉ ቀውሱን በፍጹም ጋብ ሊያደርጉት አልቻሉም። ሁኔታውም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ በባንኮች መሀከል የሚደረገው የእርስ በርስ መበዳደር( Inter Bank Lending) መተማመንን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰው መጥቷል። በባንኮች መሀከል የገንዘብ ፍሳሽ ቀውስና(Liquidity Crisis)  በተለይም ደግሞ ባንኮች ለማዕከለኛና ለትናንሽ ኩባንያዎች የሚያበድሩት ገንዘብ ስለቀነሰ እንደ 1929 ዓ.ም ዐይነቱ ቀውስ እንኳ ባይሆን በቀላሉ ሊገታ የማይችል ቀውስ በመከሰት ብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ሊያዳርስ ይችላል ተብሎ ስጋት ደርሷል። በመሆኑም በሰራተኛው ገቢና በአሰሪዎች ትርፍ መቀነስ፣ በፍጆታ ዕቃ ጥያቄ መቀነስና በምርት እንቅስቃሴ መቀዝቀዝ፣ ከዚያም አልፎ በአክስዮን ገበያ ላይ የሚሽከረከረው ገንዘብና የአክስዮን ዋጋ መቀነስ ራሱ(Stock Market Value)፣ ርስ በርሱ የተያያዘ ሰንሰለት በአንዳች ምክንያት ብጥስጥሱ እንደሚወጣና መልሶ ለመገጣጠም እንደሚያስቸግር ሁሉ፣ የአሁኑ የፋይናንስ ገበያ ቀውስና ውጤቱ በቀላሉ እርማት እንደማይገኝላቸው ይነገራል። እንዲያውም ብዞዎች ሶሻሊዝም እንዳለቀለትና መሳቂያም እንደሆነ ሁሉ፣ ሃያ ዐመት ያህል ካለምንም ተወዳዳሪነት ዓለምን ሲያሽከርከር የከረመው፣ በተለይም የአሜሪካን ካፒታሊዝም ከእንግዲህ ወዲያ በድሮው መልኩ አለመስራቱ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ አሜሪካ እንደ ቀድሞው ሶቭየት ህብረት ኪሳራ እንደሚደርስበት የኢኮኖሚ ታሪክ አዋቂዎችና የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኚዎች በሰፊው እየጻፉና እየተናገሩ ነው። ከዚህ በመነሳት ለዛሬውም ሆነ ለጠቅላላው የስርዓት ቀውስ ምክንያት ወደ ሆኑ ነገሮች በዝርዝር ገባ እያልን እንመልከት። የዛሬውን የግሎባል ኢኮኖሚ ቀውስ መረዳት ማለት ደግሞ የህብረተሰብአችንን ሁኔታና የወደፊት ዕድል ከግሎባል ኢኮኖሚ በሻገርና ውስጥ እንዴት አድርገን መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚህ ዐይነቱን ቀውስም እስከየት ድረስ መቋቋም እንችላለን ብሎ መወያየቱና ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጡ ጠቃሚ ነው ብሎ ይህ ጸሀፊ ያምናል።

ልቅ የፋይናንስ ገበያና የተወሳሰበ ሀብት የማሸጋሸጊያ ዘዴዎች !!

          ዛሬ በማያጠራጥር ሁኔታና በሁሉም፣ ይህንንም ሆነ ያኛውን የኢኮኖሚ ቲዎሪና ርዕዮተ-ዓለም እንከተላለን በሚሉ ምሁሮች ዘንድ የተደረሰበት ስምምነት፣ በተለይም ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ልቅ እየሆነ የመጣው የፋይናንስ ገበያና በየጊዜው ለራሳቸው ለፈጣሪዎቹም እንኳ ግልጽ ያልሆነ በሂሳብ ሞዴሎች ያሸበረቀ የሀብት ማሸጋሸጊያ ዘዴ መፈጠሩ ለአሁኑ ቀውስ ዋና ምክንያት መሆኑ ታምኖበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከመንግስትና ከባንክ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ የፋይናንስ ገበያዎችና የሂሳብ ዘዴዎች መፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ ተዋናይ ምሁራን ብቅ ማለታቸውና የኖብል ዋጋ ተሸላሚ መሆናቸው፣ አብዛኛዎችን የንግድም ሆነ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮችን በማሳመን ለዛሬው የኢኮኖሚ ቀውስ እንደ ተጠያቂ መሆናቸው በግልጽ ይነገራል። በተለይም በአሜሪካን የሚወጡ አዳዲስ የፋይናንስ ማቲማቲክ ሞዴሎችና የሰራተኛውን ሁኔታና ከረዢም ጊዜ አንፃር እየታየ የምርትን እንቅስቃሴ ማካሄድ ሳይሆን፣ የተካፋይ ባለሀብቶችን ጥቅም ከፍ ለማድረግ(Share Holder Value) የተወሰዱትና የሚወሰዱት እርምጃዎች፣ እንዲሁም ይህንን ለማረጋገጥና ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ በየጊዜው ታትመው የሚወጡት የማኔጂሜንት ኢኮኖሚክስ መጽሀፎች፣ የካፒታሊዝምን ዕድገት ወይንም የገበያ ኢኮኖሚ ልዩ ገጽታ እንደሰጡትና፣ ባለፉት ሃያ ዐመታት በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሀብት መሸጋሸግና በጥቂት ሰዎችና ኢንስቲቱሸኖች ዘንድ የሀብት ክምችት እንዲፈጠር ማድረግ እንደቻሉ የሚወጡት ጥናቶችና ምርምሮች ያመለክታሉ። በተለይም የዚህ ዐይነቱ የተዛባ የሀብት መሸጋሽግ አባት የሆነው አሜሪካ፣ በሀብታምና በደሀ፣ ወይም መጠነኛ ገቢ ባለቸው ሰዎች መሀከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ አካባቢዎች የሶስተኛው ዓለም ሁኔታ እየተፈጠሩና መንገድና ፓርክ ውስጥ የሚያድሩ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ እንደመጣ ሁኔታውን ለተከታተለ ሊገነዘብ ይችላል። ይህ ብቻ አይደለም። በተለይም የሪፓብሊካን ፓርቲ መሪዎች በአስተሳሰባቸው ልክ የአፍሪቃን ፖለቲከኞች ዐይነት ባህርይና ጭካኔ በማዳበርና በሎቢሰቶች ጉያ ስር በመውደቅ የኢኮኖሚውን ሁኔታና የህብረተሰቡን አኗኗር እንዳዘበራረቁ ትችታዊ አመለካከት ባላቸው ምሁሮች በየጊዜው በዜና ማሰራጫዎች ይነገራል። ህብረተሰባቸውን በስምምነት(Consensus) መርሆች ላይ በተመሰረተ መንፈስ ከማስተዳደር ይልቅ፣ ተወዳድሮ ያሸነፈ ይውጣ በሚልና የገበያን ኢኮኖሚ ወደ ንጹህ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ ህዝባቸውን ወደ ማይሆንና ሊወጣው ወደ ማይችለው ሁኔታ ውስጥ እየከተቱት ነው። ዓለምን በፍቅር ያሳበደው አሜሪካና ሞዴሉ ወደ ሲኦልነት እየተቀየሩ መምጣታቸውን የሚያመለክቱና የሚያረጋግጡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ጽሁፎችና መጽሀፎች ወጥተው ጉዱን እንድንረዳ እየጋበዙን ነው።

       ባለፈው „ግሎባላይዜሽንና መዘዙ…“ በሚለው ጽሁፌ ላይ እንዳመለከትኩት፣ የአሜሪካን ዶላር ከወርቅ ጋር የነበረው የጠበቀ ግኑኝነትና ፣ በተለይም የምዕራብ አውሮፓ ዋና ዋና የመገበያያ ገንዘቦች(Currencies) በተወሰነ ክልል ውስጥ መሽከርከርና የገንዘብ ካፒታል እንደ ልብ ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ መንቀሳቀስ አለመቻል እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ለካፒታሊዝም „ጤናማ “ በሆነ መልክ መስራት አመቺ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበር ነው። ይህንን አስተያየት ብዙ ኤክስፐርቶች ያረጋግጠሉ። ይሁንና ካፒታሊዝም ባለው ውስጠ-ኃይል(Dynamism)መሰረት ደግሞ በተገደበ ሁኔታ ዓለምን ሊያዳርስና ገበያዎችንና የጥሬ-ሀብቶችንም ሊቆጣጠር እንደማይችል ልሹ በየሃገሮች ውስጥ የተከሰተውን የገንዘብን ዕድገትና ሂደት ሁኔታ፣ እንዲሁም የክሬዲት ገንዘብ(Credit or Fiat Money) አፈጣጠርን ለተመለከተ፣ እ.አ በ1971 የዶላር ከወርቅ ጋር ያለው ግኑኝነት መላቀቅ ሎጂካል እንደሆነ ወዲያውኑ ሊገነዘብ ይችላል። በሌላ አነጋገር፣ ካፒታሊዝም ከፍተኛ ውስጣዊ-ኃይል ያለውን ያህል ራሱንም ሊያጠፋ የሚችልባቸውንም መሳሪዎች ያዘጋጃል። ይህ ዐይነቱ የካፒታሊዝም ቀውስ ደገሞ በታሪክ ውስጥ ከአንዴም ሶስቴም በላይ ታይቷል።

        የዛሬውን ዓለም አቀፋዊ የካፐታሊዝም ዕድገትና መስፋፋት፣ በተለይም የፋይናንስ ገበያን መወሳሰብ ለተመከተ ልዩና ከምን ግዜውም የበለጠ በቀላሉ ተሰባሪ የሆነ ውስብስብ ሁኔታ ተፈጥፘል። አሁን በሚታየው በተለያዩ መልኮች በልዩ ልዩ ሃገሮች ውስጥ ሰርጎ የገባው ካፒታሊዝም ህብረተሰብን መገንቢያ ሳይሆን ለጊዜው ገንዘብ ማሽከርከሪያና ሀብት ማሸጋሸጊያ መሳሪያ በመሆን የዓለምንም ገበያም ሆነ ብዙ ህብረተሰቦችን እያናጋ ለመሆኑ የሚወጡት ትችታዊ አመለካከት ያላቸው ትንተናዎች ያረጋግጣሉ። በታሪክ ውስጥ የገንዘብ ዕድገት ዐይነተኛ ባህርይ የምርትን ክንዋኔና የንግድን እንቅስቃሴ ለማገዝና ለማፋጠን ነበር።  የዛሬው የገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍናና፣ በተለይም ደግሞ የገንዘብ ሚና በገንዝብ አማካይነት ምርት ማምረትና ትርፍ ማካበት ሳይሆን፣ ገንዘብን በማሽከርከር፣ በገንዘብ አማካይነት ብዙ ገንዘብ ማፍራትና ይህንንም ለማገዝ የተለያዩና ለብዙ ሰዎች በቀላሉ ግልጽ የማይሆኑ መሳሪያዎች በመፍጠር ከየቦታው ገንዘብ ለመቃረምና ብዙ ትርፍ ለማግኘት ነው። ስለዚህም እ.አ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ መልክ የሚገለጹት የፋይናንስ መሳሪዎች ወይንም ራሳቸው አመንጪዎቹ በማቆላመጥ የፋይይናንስ ምርት(Finacial Products) የሚሏቸው በመሰረቱ ከምርት ክንውንና ከተጨባጭ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በምንም ዐይነት የተያየዙ አይደሉም። በዚህም ምክንያት የዛሬው የፋይናንስ ገበያና በዚህ አማካይነት ከየሃገሮች እየሸሸ ቀረጥ የማይከፈልባቸውና መንግስታዊ ቁጥጥር የሌለባቸው ሃገሮች ወይም ደሴቶች የሚቀመጠው ገንዘብ ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ ሆኗል ማለት ይቻላል። ለዚህ የገንዘብ መሸሽ ደግሞ የኢንቬስትሜንት ባንኮችና ሄጅ ፈንድስ ብቻ ሳይሆኑ ተጠያቂዎች፣ ራሳቸው የንግድ ባንኮችም በርካሽ ወለድ ከህዝብ የሚመጡትን ገንዘብና የሚያካብቱትን ለዚህ የቁማር መጫወቻ በማዋላቸውና ባንኮችን ወደ ካሲኖነት በመለወጥ ለቀውሱ መከሰት ተጠያቂዎች ናቸው። ይህንን የመሰለ የቁማር ጨዋታ እንዲስፋፋ ህጋዊ ያደረጉ የምዕራብ መንግስታትም ከተጠያቂነት የሚያመልጡ አይሆኑም። ይህንን በሚመለከት፣ በዚህ ህጋዊ ድርጊት የተካፈሉ ፖለቲከኞት አጥፊነታቸውን እያመኑና ቶሎ ርማት እንዲደረግ እየወተወቱ ነው። በዚህም ምክንያት የዛሬው ካፒታሊዝም በቀላሉ ሊገራ የማይችል ስርዓት እንደሆነና፣ ግራዉም ቀኙም ከዚህ የባሰ ቀውስ ከመድረሱ በፊት ርብርቦሸ መደረግ እንዳለበት እየወተወቱ ነው።

        ኤንቬስትሜንት ባንኮችና ሄጅ ፈንድስ የሚባሉት የሚንቀሳቀሱት በመሰረቱ በራሳቸው ገንዘብ ወይም ካፒታል ብቻ አይደለም። በአንድ ጊዜ በብዛት ለመጫወትና ብዙ ገንዘብም ለማትረፍ ሲሉ አስተማማኝ(Risk) ያልሆነ የቁማር ጨዋታ ይጫወታሉ። ስለሆነም በነሱ የአሰራር ደንብ መሰረት ይህ አስተማማኝ ያልሆነ ሁኔታ ብዙ ባንኮችና ኢንቬስተሮች ትከሻ ላይ(Risk Dispersion) ይጫናል። የጭነቱ ተሸካሚዎች ብዙ ሃገሮች ወይም ባንኮች እንዲሆኑ በማድረግ ትርፍ ካገኙ በብዛት ያገኛሉ፤ ወይም ደግሞ ከከሰሩ ገንዘቡ እንዳለ ይሟጠጣል። ይህ „ትንሽ ዱቄት ይዘህ ብዙ ዱቄት ወደ ላው ተጠጋ“ እንደሚባለው አነጋገር ፣ ሄጅ ፈንድስ የሚባሉት፣ ለምሳሌ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ካላቸው በተጨማሪ እስከ መቶ ቢሊዮን የሚጠጋ ከሌሎች ይቃርማሉ። ይህ ዐይነቱ የቁማር ጨዋታ አንድ ትንሽ ሁኔታን በጣም ከፍ ማድረግ ያሰፈልጋል በሚለው ደንብ መሰረት(Leverage) ኤንቬስትሜንት ባንኮች ወይም ፈንድስ በብዙ ገንዘብ የሚተመን ቋሚ ሀብት ሳይኖራቸው በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር በብድር በመውሰድ ወይም ሌሎችንም የጨዋታው ተካፋይ በማድረግ እንደ ውርርዱ ዐይነት የከሰረው ይከስራል። ሌላው ደግሞ ብዙ ገንዘብ ያገኛል። ምክንያቱም ይህ ገንዘብ በቀጥታ ከምርት ጋር ያልተያያዘና  ውርርድ እንደመሆኑ መጠን፣ ገንዘብን በገንዘብ ማትረፍ የሚቻለው አንዱ ሲጠቀምና ሌላው ሲጎዳ ብቻ ነው። ይህም ማለት የዚህ ዐይነቱ ቁማር ጨዋታ የዜሮ ድምር(Zero-Sum)  ዐይነት ጨዋታ ነው ማለት ነው። በዚህ መልክ በተለይም በዚህ ሚሌኒዩም መግቢያ ለይ ኤንተርኔትና ከዚህ ጋር የተያያዙ የማገልገሊያ መሳሪዎች( Dot Coms) በተስፋፉበት ወቅት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የዋህ ህዝቦች የገበያው ተካፋይ እንሆናለን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብት እናካብታለን እያሉ በባንክ ሰራተኞች አማካሪነትና አጭበርባሪነት ከቁጠባ ደብተራቸው ገንዘባቸውን ያሸጋሸጉና የአክሲዮን ወረቀት የገዙት በሙሉ ሶስት አራተኛ የሚሆነውን ገንዘባቸውን እንዲያጡ ሆነዋል። ልክ እንደ ሄጅ ፈንድስ ብዙም ከበስተጀርባው ቋሚ ሀብት ሳይኖራቸው ብዙ የአክሲየን ወረቀት በመበተን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከየዋሁ ህዝብ በመምጠጥ የደለቡትና በኋላ ድምጥማጣቸው የጠፉት የአዲስ ገበያ(New Economy= Dot Coms) ተዋናዮች ለፋይንስ ገበያው መስፋፋት ራሳቸውን የቻሉ ዐይነተኛ ምክንያት ሆነው ነበር።

        ወደ ሄጅ ፈንድስና ወደ ኢንቬሰትሜንት ባንኮች ስንመጣ ግን፣ እነዚህኞች ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን፣ ባንኮችን፣ ተመሳሳይ ኢንሰቲቱሽኖችን፣ ለምሳሌ እንደ ደህንነት(Insurance Companies) የመሳሰሉ ኩባንያዎችንና በቁማሩ ውስጥ ለመጫወት የገቡትንም ሃገሮች ኢኮኖሚ ማናጋት እንደሚችሉ ነው። በዚህም መሰረት እ.አ በ1998 ዓ.ም የረዢም ጊዜ መዋዕለ-ነዋይ(Long Term Capital Investment=LTCM) በመባል የሚታወቀውና፣ እንደ ጀርመን የመሳሰሉት ትላልቅ ባንኮች ሳይቀሩ የተካፈሉበትና በሁለት የኖቭል ዋጋ ተሸላሚዎች የተቋቋመውና ይተዳደር የነበረው የቁማር መጫወቻ የፋይናንስ ገበያ በደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ በጊዜው ጠቅላላውን የፋይናንስ ገበያ ሊያናጋ ሲል በአሜሪካን የፌዴራል ባንክ አነሳሸነትና በሌሎች ደራሺነት ነው ከመናጋት ወይም ከመፈራረስ ሊድን የቻለው። በሌላ በኩል ግን በዚሁ ዘመን የራሳቸውን ገንዘብ በተለይም ከዶላር ጋር ያገናኙና እንደ ገበያው ሁኔታ ገንዘባቸውን ተለዋዋጭ ያደረጉ እንደ ታይላንድ፣ ኢንዶኔሺያ፣ ማሌሺያና ደበቡ ኮሪያ የመሳሰሉ ሃገሮች የመንግስት ወረቀቶችን በመሸጥና ከካፒታል ገበያ ላይ ገንዘብ በመቃረም የሰሩት የመኖሪያም ሆነ ሆቴል ቤቶች  በአጭር ጊዜ ውስጥ ተካፋዮችን ሀብታም ካደረገ በኋላ ዋጋው ዝቅ እያለ ሲመጣ እንደ ጆርጅ ሶሮን የመሳሰሉት የገበያውን ሁኔታ ተመልከተው ገንዘባቸውን ሲያወጡ ብዙ ሰው ወደ ድህነት አዘቅት ተገፍትፘል። የእነዚህ ሃገሮች ኢኮኖሚ ዕድገትም በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንዲል ተገዷል። ይሁንና ግን በዚያን ጊዜ የእነዚህን ሃገር ኢኮኖሚዎች ለማዳን የተወሰደው እርምጃ ወገባቸውን የባሰውኑ እንዲያጠብቁ ነው ያስገደዳቸው። እነ አይ ኤም ኤፍ የመሳሰለት ድርጅቶች መሪር ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የቻሉበት ሁኔታ ተፈጠረላቸው። በሌላ በኩል በየጊዜው እንደዚህ ዐይነቱ ቀውስ በኢንዱስትሪ ሃገሮች ሲከስት ተግባራዊ የሚሆነው ፖሊሲ ለየት ይላል ማለት ነው ። ሆኖም ግን እንደዚህ ለየት ያለው ፖሊሲ ደግሞ ሰሞኑን እንደምናየው ቀውሱን ጋብ ሊያደርገው አልቻለም። በብዙ መቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ ቢፈስም ይህ ገንዘብ ወዴት እንደደረሰ ማወቅ በፍጹም አይቻልም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ ቀውስ በሚከሰትበት ወቅት ከውስጥ ለጊዜውም ቢሆን ጋብ እንዲል የኢንዱስትሪ ሃገሮችና የማዕከላዊ ባንኮች የሚወስዱት እርምጃዎች ለፋይናንስ ገበያው ለጊዜው እስትንፋስ ቢሰጠውም አሁን እንደምናየው ቀውሱ ከገበያው አልፎ ህብረተሰበአዊ ቀውስ እየፈጠረና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ራሳቸው በአንድ ወቅት በቁማር ጨዋታው ደልበው የሚሰሩትን ያጡ የፋይናንስ ገበያ አማካሪያዎችና ደላሎች፣ አንዳንዶቹ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሲገድሉ፣ ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ የህሊና ቀውስ እንደደረሰባቸው የዜና ማሰራጫዎችን ለተከታተለ ሊገነዘብ ይችላል።

          የቁማሩ ዐይነትና ጨዋታ ልዩ ልዩና የገንዘብን መሽከርከር በከፍተኛ ደረጃ የሚያፋጥን ነው። በተለይም አላን ግሪን ስፓን የፌዴራሉ ባንክ አስተዳዳሪ መሆን ከጀመሩበት ጊዜና ከወል ስትሪት ሰራተኞች ጋር ያላቸው ግኑኝነት እየጠበቀ ከመጣ ወዲህ የተከተሉት ዝቅተኛ የወለድ ፖሊሲ ገንዘብን ወደ ፋይናንስ ገበያ ወይም የካፒታል ማርኬት ላይ እንዲፈስ አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። በዝቅተኛ ወለድ ፖሊሲ መሰረት፣ ካፒታል ከምርት ክንውንና ኢንዱስትሪዎችን ከመትከል ይልቅ ቶሎ ቶሎ ትርፍ ወደ ሚያመጣበት ወደ ቁማር ጨዋታነት ቦታ እንዲውል ተገደደ። በአላን ግሪን ስፓን ልቅ የገንዘብ ፖሊሲ ወለዱ ከ2001 እስከ 2003 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ከ6.5% ወደ 1% ዝቅ በማለት የካፒታል ገበያውን ሊያጥለቀልቅና የቁማር ጨዋታው እንዲጦፍ አመቺ ሁኔታ ፈጠረለት። በተጨማሪም የጃፓን ማዕከላዊ ባንክ ለብዙ ዐመታት የተከተለው ወደ አልቦ የሚጠጋ የገንዘብ ብድር አሰጣጥ፣ በተለይም በዓለም ገበያ ላይ በወለድ ልዩነት በሚፈጠር ገቢና በከረንሲዎች ልውውጥ አማካይነት የሚገኝን ትርፍ በመጠቀም ቁማር ተጫዋቾች ከጃፓን በዝቅተኛ ወለድ በመበደርና ወደ ዶላር በመቀየርና ወለዱ ከፍ ወዳለበት ቦታ በማሸጋገር የገንዘቡን መሽከርከር ለማፋጠንና ገበያውም ከምንግዜውም በላይ እንዲጦፍ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ዐይነቱ በሁለት ከረንሲዎች መሀከል ያለውን የወለድ ልዩነት ተገንዝቦ ገንዘብ መበደርና ከፍተኛ ወለድ ወዳለበት አካባቢ ኢንቬስት ማድረግ ኬሬ ትሬድ(Carry Trade) በመባል ይታወቃል። ለገንዘብ ወይም ለፋይናንስ ገበያው መጧጧፍና ልዩ ልዩ ሀብት ማካበቻ ዘዴ መፈጠር የዘይት አምራች ሃገሮችም የበኩላቸውን አስተዋጽዎ አድርገዋል። በዘይት ሺያጭ የሚያገኙትን ትርፍ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሃገሮቻቸው ኢንቬስት ለማድረግ ባለመቻለቸውና በተለይም ለንደንና የአማሬካን ባንኮች ውስጥ ማሰቀመጣቸው ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እምርታ ሰጥቶታል። ከዚህም በላይ የቻይና በዶላር መጥለቅለቅ፣ ዓለም አቀፋዊ ተዋናይ መሆንና ትርፉን ዶላር ወደ አሜሪካን ባንኮች አስተላልፎ የመንግስት ወረቀትና( Bonds and Certficates) በተለይም የኢንቬስትሜንት ባንኮች ተካፋይ መሆን የካፒታል ገበያው እንዲያብጥ አድርጎታል። ራሺያና አንዳንድ ሃገሮችም፣ ሃገሮቻቸው ውስጥ ገንዘባቸውን ኢንቬስት በማድረግ ከተማዎችን ከመገንባትና ኢንዱስትሪዎችን አቋቁመው የስራ ዕድል ከመፍጠር ይልቅ በዚህ የቁማር ጨዋታ ተካፋይ በመሆን ለገበያው ዕብጠት ተጠያቂ ናቸው ማለት ይቻላል።

         ያሁኑን የፋይናንስ ገበያ ቀውስ ዐይነተኛ የሚያደርገው ብዙ ባንኮችና ሃገሮች በአንድ የፋይናንስ ምርት(Financial Product) ላይ መረባረባቸውና በዚህ ላይ መተማመናቸውና ብዙም ትርፍ እናተርፋለን ብለው የራሳቸውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን በተለያየ መልክ የተቀመጡ የህዝብ ገንዘቦችንም ወደዚህ ዐይነቱ ቁማር ጨዋታ ማዘዋወራቸው ነው። በላፈው ጽሁፌና ከዚህ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው፣ በብድር አሜሪካን የተሰሩ ቤቶች የብዙ አበዳሪ ባንኮችን ዐይን እንዲታወር ያደረጉና ያታላሉ ሲሆን፣ ለአሁኑ የፋይናንስ ቀውስ እንደዋና ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው። ምክንያቱም ሁሉም ባንኮች ይህ ዐይነቱ የቁማር ጨዋታ ብዙ ትርፍ ያመጣልናል ብለው በመገመት ያለ የሌለ ገንዘባቸውን ወደ ዚሁ የብድር ቤት ገበያ ላይ(Sub-prime market) አስተላልፋዋል። በመስከረም ወር 2006 ታትሞ በወጣው „The Economist“ የሚባለው የእንግሊዙ መጽሄት መሰረት፣ የቤት ስራ የጦፈበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤቶች ዋጋ ከሰላሳ ቢሊዮን ወደ ሰባ ቢሊዮን ዶላር እንዲተኮስ ያደረገ የገበያ ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በዚህ መልክ እያደገና እየተስፋፋ የመጣው ፣ እንዲሁም ደግሞ በጠያቂው ብዛት ዋጋው እየጨመረ የመጣ የቤት አስራርና ቤቶችን ገዝቶ የጥፍ እጥፍ መሽጥ-እ.አ ከ1997 እስከ 2007 ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ የቤት ዋጋ በ500% አድጓል- ወይም ማከራየትና በወለዱ መጠቀምና ከፊሉን ደግሞ ለባንክ ዕዳ መክፈል እንደ ልዩ ሀብትና ትርፍ ማካባቻ ዘዴ ሆኖ የታየበት ሁኔታ ነበር። በመጀመሪያው ወለዱ ርካሽ በነበረበት ወቅት ገንዘብ ተበደሮ ቤት መስራትም ሆነ መግዛትና ዕዳውን መክፈል ቀላል የመሰለውን ያህል፣ ወለዱ በመጀመሪያው ወቅት በነበረበት ሁኔታ ሳይሆን ከፍ እያለ ሲሄድና ለተወሰነ ጊዜም ዋጋው ከፍ እያለ ሄዶ በኋላ ላይ ዝቅ እያለ እንዲሄድ የተገደደው የቤት ሸያጭ ዋጋ ተበዳሪዎችንም ሆነ አበዳሪዎችን ወይም ደግሞ ኢንቬስተሮችንም ወደ መምታትና እንደተጠበቀው ገንዘባቸው ሊመለስ ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጠረ። ለምሳሌ የቤት አሰሪዎች ባንኮች (Morgage Banks) ቤት ለመስራትም ሆነ በዚህ ገበያ ላይ ለመሳተፍ ከሌላ የንግድ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ካሉ ባንኮች ይበደራሉ ወይም ደግሞ ይገፚፚቸዋል። በሌላ በኩል ሰብ-ፕራይም ገበያ ላይ ኤንቭስት ያደረጉት ኢንቬስትሜንት ባንኮች እንዳይከስሩ ለቤት መስሪያ ያበደሩትን ገዘብ እንደመዋዕለ-ነዋይ አድርጎና ተመላሽ አድርጎ በመገመትና ይህ ብድር ራሱ ተጠቃልሎ የአክስዮን ገበያ እንደሚሸጠው የድርሻ ወረቀት ዐይነት ሌሎች እንዲገዙት ይደረጋል።ይህ ዐይነቱ የብድር አሰጣጥና ብድሩን በወረቀት(Certificats) አማካይነት ሌሎች እንዲካፈሉበት የማድረግ ስትራቴጄ ተጨማሪ የዕዳ ክፍያ ግዳጅ(Collateralized Debt Obligations=CDO) በመባል ይታወቃል። በዚህ ዐይነት ዘዴ ዋናዎቹ አበዳሪ ባንኮች ዕዳውን ለሌላ በማስተላለፍና ሸክማቸውን በማቃለል ብዙ ሃገሮችና ባንኮች የኪሳራው ወይም አስተማማኝ ያልሆነው የቁማር ጨዋታ ተካፋይ ይሆናሉ ማለት ነው። የሞርጌጅ ባንኮች ደግሞ እርግጠኛ ለመሆናቸው ከነሱ ጋር የተሳሰሩ የገበያውን ሁኔታና ዕድገት የሚያጠኑ(Rating Agents) ስለ ገበያው ሁኔታ በቻርትና በመሳሰሉት ጥናቶች በማታለል በገበያው ላይ የተካፈለ ሁሉ ብዙ ትርፍ እንደሚያተርፉና እንደሚከብሩ ያሳምናሉ። በዚህ መልክ የብዙ ዐመታት የባንክ ልምድና አሰራር ቴክኒክ ዕውቀት ያላቸውና የገበያውንም ሁኔታ ለመገመት የሚችሉ በመታወር ዛሬ የምንመለከተውን ሁኔታ እንዲፈጠር አስተዋጽዎ ለማድረግ ችለዋል። ለምሳሌ፣ በዚህ መልክ በጀርመን በየክፈለ ሃገሩ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙትና ተግባራቸው ቁማር መጫወት ሳይሆን ለማዕከለኛና ለትናንሽ ኢንዱስትሪዎች ብድር ሰጪዎች የሆኑትን ባንኮች ትተን በጣም ትልቅ የሚባለውን በልዩ ልዩ ህንጻ ስራ የተሰማራውን ሪል ስቴት(Real State) የሚባለውን ባንክ ብንወስድ አሜሪካን ሰብ-ፕራይም ገበያ ላይ በመካፈሉ ወደ ሃምሳ ቢሊዮን የሚጠጋ ኦይሮ ከስሯል። በዚህ ብቻ ሳይወሰን ለጡረታ የተቀመጡ ገንዘቦች ሁሉ ወደ ዚህ ቁማር መጫወቻና አስተማማኝ ያልሆነ ገበያ ላይ በመዋላቸው የብዙ ሰዎች ሀብት እንዳለ ተሟጧል። በዚህ ምክንያት ይህ ቀውስ ከአሜሪካ አልፎ ወደ አይስ ላንድ፣ ወደ እንግሊዝና አየር ላንድ፣ እንዲሁም ደግሞ ወደ ጀርመንና የስዊዝ ባንኮች በመሸጋገርና የቤልጂግንና የሆላንድ ባንኮችን በመዳሰስ እንዳለ የምዕራብ ሃገሮችን የማይበገር የሚመስለውን ኢኮኖሚ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እያናጋውና በተለያዩ የመጠጋገኛ መሳሪዎችም ሊጠገን ወደ ማይችልበት ሁኔታ እየገፈተረው ነው። በዚህ ቀውስ ምክንያት የተነሳ ምንም ሳይሰራ ሀብት ያካበተው አዲሱ የራሺያ ኦሊጋርኪ መደብም ባጭር ጊዜ ውስጥ 240 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶበታል። ይህ ቀውስ በእዚህ እንዳለና የብዙ ሰዎችም ገንዘብ ጠፍቶና አሁንም ቢሆን የዕዳው ተሸካሚ ራሱ ተጎጂው ህዝብ እንጂ ለዚህ የፋይናንስ ገበያ ተጠያቂ የሆኑት የባንክ ማኔጀሮች አይደሉም። ምክንያቱም መንግስታት ባንኮችን ለማዳን የሚወስዱት እርምጃ ሁሉ አዲስ ገንዘብ በማተም የሚያገግም ሳይሆን፣ ከህዝቡ በሚገኘው ቀረጥ ብቻ ነው ሊስተካከል የሚችለው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ትርፍን ግላዊ፣ ዕዳን ደግሞ ህዝባዊ ማድረግ ይባላል። በሌላ ወገን ግን ማኔጀሮች በመዝናናት የህዝብና የሚዲያው ግፊት ሲብስባቸው ስራቸውን ተገደው ከመልቀቅ በስተቀር እስካሁን ድረስ በህግ የተጠየቁበት ሁኔታ የለም።

       በዚህ መሰረት የአሜሪካን መንግስት በፋይናንስ ሚኒስተሩ በሚሰተር ፓውልሰንና በፌድ ዋና አስተዳዳሪ በፕሮፌሰር በርናንከ ገፋፊነትና በቻይና ጣልቃ-ገብነት ባንኮችን ለማዳን ሲባል ወደ 700 ቢሊዮን የሚያክል ዶላር ወደ ባንኮችና ወደ ሄጅ ፈንድሰ ፈሷል። የእንግሊዝ መንግስት ደግሞ ከእንደዚህ ዐይነቱ ድጋፍ ባሻገር ባንኮችን በግማሽ ጎናቸው በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ እርምጃ ወስዷል። ባንኮችም ከእንግዲህ ወዲህ እንደፈለጋቸው የቁማር ጨዋታ እንዳይጫወቱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን የአሰራር ዘዴያቸውንም ግልጽ እንዲያደርጉና በጥንታዊ የባንክ አሰራር ህግ መሰረት እንዲተዳደሩ ህጎች በመርቀቅ ላይ ናቸው። እንደምናየው ግን ባሁኑ ወቅት በገበያው ዘንድ አለመተማመንን እየፈጠራና በተለይም የክሬዲትን ገበያው እያናጋው ነው። ይህ አለመተማመን ከቀጠለና ባንኮች ርስ በርስ መበዳደራቸውን ካቆሙ ወይም ካቀዘቀዙ ደግሞ ጠቅላላው የክሬዴት ገበያ እንደሚናጋና የምርትም ሆነ ፍጆታን በብድር ገዝቶ የመጠቀም ሁኔታና ክንውን እንደሚዳከም ኤክስፐርቶች ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ለፍጆታ እቃዎች ግዢ የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስና ገንዘባቸውን ከአክስዮን ወደ ተራና ብዙ ወለድ ሊያስገኝ የማይችል፣ ግን ደግሞ እርግጠኛ ወደ ሆነ የቁጠባ ደብተርና የመንግስት ወረቀቶችን(Bonds) በመግዛት ሀብታቸውን በማሸጋሸግ ላይ ናቸው።

የብድር አሰጣጥና መዘዙ

        የዛሬውን የፋይናንስ ገበያ ቀውስ ለመረዳት መሰረታዊ ነገሮችን እያነሳን መወያየት አለብን። ካለበለዚያ የቀውሱን ምንነትና ውስጣዊ ህግ መረዳት አንችልም። በመሰረቱ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ የምርት ክንውን ከትርፍ አንጻር የሚታቀድ ልዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው። ምርትን ለማምረት፣ አዳዲስ የምርት መሳሪያዎችን ገዝቶና ተክሎ ምርትን በጥራትም ሆነ በብዛት ለማምረትና በገበያ ላይ ሸጦ ትርፍ ለማትረፍ የግዴታ አምራቾች በራሳቸው ካፒታል ብቻ ሊመኩ አይችሉም። የገበያው ውድድር ሁኔታ፣ በተለይም ማዕከለኛ እንዱስትሪ ያላቸውን ከባንክ ተበድረው ኢንቬስት እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። በዚህ ዐይነት በባንኮች፣ በአምራቾች፣ በነጋዴዎችና በጥሬ-ሀብት አቅራቤዎች መሀከል መተሳሰር ይፈጠራል። ከሞላ ጎደል ባንኮች ባላቸው የገንዘብ ኃይል የኢንድስትሪዎችን ዕድገት፣ የመኖርና ያለመኖር ሁኔታ ይወስናሉ ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የሚመረተው ምርት በሙሉ መሸጥ አለበት። አምራቾችም ሆኑ ነጋዴዎች ትርፍ ሊያተርፉ የሚችሉት በቂ የሚገዛ ሰው(Effective Demand) ሲኖር ብቻ ነው። ይሁንና ግን አብዛኛው ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ደግሞ በየወሩ በሚያገኘው ገቢ ከቤት ኪራይና ከቀን ተቀን ወጪ ተሻግሮ ቤት መስራት ወይም መኪና መግዛት አይችልም። በዚህም መሰረት የሚመረቱት ምርቶች፣ በተለይም እንደ ኤሌክትሮኒክስና መኪና የመሳሰሉት ወይም ደግሞ ቤት መስራትም ሆነ መግዛት የመሳሰሉት በየወሩ በሚከፈል ዕዳ(Installment) ነው በጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉት።  ይህ ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምና፣ በተለይም ከ1970ዎቹ ዓመታት ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው አመራረትና የፍጆታ እቃዎች አጠቃቀም ለካፒታሊዝም ዕድገት እምርታ መሰጠቱ ብቻ ሳይሆን ብድር ዋናው የካፒታሊዝም የደም ስር በመሆን ህይወቱን ወሳኝ ሆኗል። የምርት እንቅስቃሴው ካለብድር ሊሸከርከር በፍጹም አይችልም ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ የብድር አሰጣጥ ዘዴና፣ ብድር ተበድሮም ማምረትና የፍጆታን እቃ መጠቀም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ ነው ጠቃሚነቱ። ምክንያቱም ሁሉም አምራች ኃይል በገበያው ላይ ብቃትነት ስለማይኖረውና ተወዳዳሪም ስለማይሆን የተበደረውን በድር መልሶ የማይከፍልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከሰርኩ ብሎ ካስታወቀ እንደ ህጋዊ ሁኔታው ንብረቱን እንዲሸጥና ዕዳውን እንዲከፍል ይገደዳል። ላባቸውን እያንጠፈጠፉ የወር ደሞዝ እያገኙ የሚተዳደደሩት ሠራተኞች ደግሞ ተትረፍርፎና ተብለጭልጮ ገበያ ላይ በሚቀርበው የሚታለሉና በየጊዜው እየገዛን እንጠቀማለን የሚሉ ከሆነ በየወሩ የሚያገኙት ገቢ እየቀነሰ ይመጣል ማለት። ቀስ በቀስም ኑሮአቸው ይናጋል ማለት ነው። ዛሬ በብዙ የካፒታሊስት ሃገሮች የሚታየው ቀውስ ወደ ቤተሰብ እየተሸጋገረ የመጣው የብድር ቀውስና አብዛኛውም ህዝብ ለመክፈል ያለው ኃይል እየተዳከመ የመጣበት ምክንያት እንደዚህ ዐይነቱ የብድር ኢኮኖሚና ፍጆታን ካለገደብ ገዝቶ የመጠቀም ሁኔታ በመፈጠሩ ነው። ራሳቸውን ጠብቀው የኖሩና በመጠነኛ የፍጀታ አጠቃቀም የሚደሰቱ ሰዎች ግን የዚህ ዐይነቱ የብደር ሰለባ አልሆኑም።

          ብድር ዋናው የካፒታሊዝም አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን ያህል በሁሉም ሃገሮች በአንድ ዐይነት ፍጥነት የሚያድግ አይደለም። በተለይም ዛሬ ህብረተሰቡንና ኢኮኖሚውን እያናጋ የመጣው በአሜሪካን ሃገር የተከሰተው የብድር አሰጣጥ ዘዴና ሠራተኞችም በወር ደሞዛቸው አስፈላጊውን ነገር ገዝተው ለመጠቀም ያልቻሉበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው። የአሜሪካ የፍጆታ ገበያ እንዳለ በበድር የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን ይህ ብድር ሲቋረጥና ተበዳሪዎችም መክፈል -አብዛኛዎቹ መክፈል የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል- የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ጠቅላላው ገበያ ይናጋል ማለት ነው። ከሰላሳና ከሃያ ዐመት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲወዳደር በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን የቤተሰብ ገቢ(House Hold Income) እየቀነሰ የመጣ እንደመሆኑ መጠን አብዛኛው ህዝብ በሚያገኘው ገቢ ከተወሰኑ ነገሮች በስተቀር ገዝቶ የመጠቀም ኃይል የለውም። ስለሆነም መቆጠብና ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ አይችልም። በዚህም ምክንያት ባንኮች ለህዝቡ የሚያበድሩት የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ያጠራቀመውንና በቁጠባ መልክ ያስቀመጠውን መልሶ በማበደር ሳይሆን ራሳቸው በሚፈጥሩት ወይንም የክሬዴት ኢንሰቲቱሽኖች ልዩ የክሬዲት ሲስተም በመፍጠርና ተጠቃሚውን የዚህ ልዩ የክሬዲት መካኒዝም ሰለባ በማድረግና በመተብተብ ነው። ይህ ዐይነቱ ልዩ የፍጆታ አጠቃቀምና የብድር አሰጣጥ ዘዴ ሰላሳ ዐመት ያህል የሰራውን ያህል ከዚያ በላይ መስራት የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣቱ ለጠቅላለው ኢኮኖሚ የጊዜ በምብ እየሆነ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በጥቂት ሀብታሞች ገቢና – ለምሳሌ የፎርድ ማኔጀር በጊዜው በዓመት 19 ሚሊዮን ዶላር ያገኝ ነበር፣ ይህ የዓመት ገቢ ሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎችን ሳያካትት ነው።-  በሰፊው ህዝብ ዘንድ ያለው የገቢ ልዩነት በብዙ እጅ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህም በላይ ብዙ ገንዘብ ስላለው ብቻ ገንዘቡን ለመንግስት በማበደርም ሆነ ካፒታል ገበያ(Capital Market) ላይ በማዋል በወለድ ብቻ የሚኖርና ከታች ወደ ላይ ገንዘብ በመንግስት ከቀረጥ በሚገኝ ወለድ እየተላለፈለት የሚኖር በጣም ጥቂት የሀብታም መደብ በመፈጠር ለጠቅላላው የሀብት ክፍፍል መነሾ በመሆን የመንግስትን ተግባር ደንጋጊ ሆኗል። በዚህ ሁኔታና በሰፈነው ያልተመጣጠነ የገቢ ልዩነትና የሰራተኛው ገቢ መቀነስና በብድር ላይ መመካት ኢኮኖሚው በቋፍ ላይ እንደተቀመጠ ከባድ እቃ አድርጎታል። ይህ ዐይነቱ የብድር ኢኮኖሚ መስፋፋትና ከውስጥ ደግሞ ልሹ መንግስት ለትላልቅ ኮርፖሬሽኖች በሚያደርገው ድጎማና የቀረጥ ቅነሳ ምክንያት ራሱም ተበዳሪ በመሆን፣ ጠቅላላው ኢኮኖሚ የብድር ኢኮኖሚ እንዲሆን አድርጎታል። ስታትሰቲኮች እንደሚያረጋግጡት፣ የቤተሰቦች፣ የኩባንያዎችና የመንግስቱ ዕዳ አንድ ላይ ተደምረው ወደ ሰላሳ አምስት ትሬሊዬን ዶላር እንደሚደርሱ ነው። በፍጹም ሊከፈል የማይችል ዕዳ ማለት ነው።

        እንዲዚህ ዐይነቱ የብድር ኢኮኖሚና ከታች ወደ ላይ የሀብት ሽግሽግ ዘዴ የግዴታ የባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ኃይል ሲያጠነክር፣ በዚያው መጠንም   በሚከተሉት ፖሊሲ የጠቅላለውን የምርት ክንውን ደንጋጊዎች ወደ መሆን ተሸጋግረዋል። በአለፉት 20 ዓመታት በግሎባላይዜሽን ስም የተካሄደው ዓለም አቀፋዊ የምርት እንቅስቃሴ የባንኮችንና ጥቂት የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ኃይል ማጠንከሩ ብቻ ሳይሆን የተወሰኑ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትንንሾችን እየጨፈለቁና እየዋጡ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር እየተዋሃዱና የነሱንም ሂደት እየወሰኑ የመጡበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ካርል ማርክስ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት፣ የአውስትሪያው ፊናንስ ሚኒስተር የነበረው ሂልፈርዲንግ ደግሞ በ1920ዎቹ ያሉትና የተነተኑት ሁኔታ ጉልህ እየሆነ መጥቷል ማለት ነው። ይኸውም የፋይናንስ ካፒታል የበላይነትን በመያዝ ጠቅላላውን ኢኮኖሚ በመቆጣጠር ላይ ነው። ስለዚህም ስለዛሬው የፋይናንስ ገበያ ሁኔታና ቀውስ በምናወራበት ጊዜ ከዚህ ዐይነቱ የባንኮች ማበጥና የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ህይወት መደንገግም ጋር ማያያዝና መመርመር አለብን ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከትና የባንኮችን ውስጣዊ ባህርይ መረዳት በተዘዋዋሪ የቱን ያህል በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይም ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው መረዳት ያስችለናል። ካለበለዚያ የቀውሱን ምንንትና መነሾ በደንብ መረዳት አንችልም ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ የተሟላ ስዕል እንዲኖረን፣ በየጊዜው የሚከሰተውን የኃይል አሰላለፍና የሚፈጠረው ርዕዮተ-ዓለም በካፒታሊዝም ጤናማ ሆኖ መስራትና አለመስራት ላይ የቱን ያህል ተፅዕኖ እንደሚኖረው ጠጋ ብሎ መመርመሩ ያስፈልጋል። ከዚያ በፊት የሚከተለውን ትንተና ጠጋ ብለን እንመልከት።

„የሚያሰፈራው ሁኔታ“

          ሰሞኑን በየዜና ማሰራጫዎቹ እንደሰማነው፣ ከመቶና ከመቶ ሃምሳ ዐመት ዕደሜ በላይ ያላቸውና የፋይናንስ ገበያውን ሲቆጣጠሩና ሲያምሱ የቆዩት ዋና ዋና ኢንቬሰትሜንት ባንኮች፣ እንደ ቢር ስተርና ሌህማን ብራዘር ከገበያ እየተስፈናጠሩ ሲወጡ፣ የተቀሩት ደግሞ አይ በመንግስትና በፌድ ድጋፍ ካሊያም ደግሞ እንደ አረብ ሃገሮች፣ ሲንጋፖርና ቻይና(State Funds) ጣልቃ-ገብነት ድጋፍ ለጊዜውም ቢሆን የከሰሩትን ከስረው በማገገም ላይ ናቸው። ብዙ ተንታኚዎች እንደሚሉት፣ በተለይም ትልቁ የስዊዘርላንዱ የኢንቬስተሜንት ባንክ(UBS) የሲንጋፖር የመንግስት ፈንድ ባይኖርና ባይካፈል ኖሮ ድምጥማጡ እንደሚጠፋ ነበር የሚናገሩት። በሌላ አነጋገር፣ እንደዚህ የመሳሰሉትን ኢንቬስትሜንት ባንኮች ማዳን የቻሉት ወይም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ህይወታቸው እንዲያንሰራራ ያደረጉት የመንግስት ፈንድ የሚባሉት ከአረብ ሃገሮች፣ ከሲንጋፖርና ከቻይና የመጡት ገንዘቦች ናቸው። በሌላ ወገን ግን ድጋፍ ያላገኙ አስራ ስድስት የአሜሪካ  ባንኮች በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከስረው ተዘግተዋል። ከዚህም በላይ ሄጅ ፈንድ የሚባሉትና በንግድ ባንኮችና በግለሰብ ሀብታሞች የሚንቀሳቀሱት የቁማር ተጫዎቾችም እየተመቱ ነው። ትርፍ እናካብታለን ብለው ሄጅ ፈንድ ላይ ካፒታላቸውን ያፈሰሱ ባንኮች፣ ለምሳሌ እንደ ጀርመን ባንክ(Deutsche Bank) የመሳሰሉትና ሌሎች ኢንስቲቱሽናል ኢንቬስተርስ-ባንኮችና ኢንሽራንስ ኩባንያዎች- ገንዘባችንን መልሱልን እያሉ በመወትወታቸው በዚያ አካባቢ የሚሽከረከረው የቁማር ገንዘብ በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ነው። ይህ በእንደዚህ እንዳለ  የፋይናንስ ገበያው ቀውስ ሰሞኑን እንደምንሰማው ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚውም በመሸጋገር ጠቅላላውን ኢኮኖሚ እየመታውና ቀውስ(Recession) ውስጥ እየከተተው ነው።

         በተለይ የአሜሪካ ኢኮኖሚ መዳከም ብዙ ዕቃ ላኪ ሃገሮችን(Export Oreinted Countries) ኢኮኖሚ እያዳከመው ነው። ለምሳሌ ቻይና በዓለም ገበያ ላይ ከምታራግፋቸው ምርቶች አርባ በመቶ ያህሉ አሜሪካን ገበያ ላይ ነው የሚራገፈው። ሜክሲኮ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት ዘጠና በመቶው ያህሉን አሜሪካን ገበያ ላይ ነው የምትሸጠው። ጠቅላላው ላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካን ተደምሮ ስድሳ በመቶ የሚሆነውን ምርት አሜሪካን ገበያ ላይ ነው የሚያራግፉት። እንደዚሁም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ በአሜሪካን ገበያ ላይ የበለጠ ጥገኛ ናቸው። ከዚህ ውስጥ እስከተወሰነ ደረጃ ሊተርፍ የሚችለው የአውሮፓ የጋራ ገበያ ብቻ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ እዚያው በዚያው የሚሽከረከርና በቅርብ ጊዜ አባል የሆኑ ሃገሮች የውስጥ ገበያቸው እየተስፋፋ ሲመጣ የመግዛት ኃይላቸውም እየጠነከረ ይመጣል። ይህም ሆኖ በተለይም በአሜሪካ ገበያ ላይ የሚመኩ በተለይም የጀርመን መኪና አምራቾች፣ እንደ ማርቼዲስና ቢ ኤም ደብልዩና አውዲ የመሳሰሉት ምርታቸውን እያቀዘቀዙና ሰራተኛውን ወደ ግዳጅ እረፍት እየላኩት ነው። በዚህም ምክንያት የአሜሪካ ገበያ መዳከም፣ በተለይም ደግሞ የክሬዴት ገበያ መዳከምም ሆነ በከፍተኛ ፍጥነት እየቀዘቀዘ መምጣት አሜሪካ እንደወትሮ የውጭ እቃ ጠያቂ እንዳይሆን ይገደዳል ማለት ነው። ይህ ለአሜሪካ ጥሩ የሆነውን ያህል፣ በአሜሪካ ገበያ ላይ የሚመኩ እንደ ጃፓንና ቻይና የመሳሰሉት ሃገሮች የምርት ክንውናቸውን መቀነሳቸው ብቻ ሳይሆን የስራ መስኩ ሊጎዳባቸው ይችላል፤ ካለበለዚያ ደግሞ የውስጥ ገበያቸውን ወደ ማደባር ስትራቴጂ ሊያመሩ ይችሉ ይሆናል፤ ወይንም ደግሞ ሌላ ወደ አፍሪቃና ወደራሳቸው የአካባቢ ገበያ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ መከተል ይገደዱ ይሆናል። ከረዢም ጊዜ ጀምሮ ያለው አዝማሚያ በአካባቢዎች አዳዲስ ገበያዎችን ማቋቋም ወይም ደግሞ ያሉትን ማጠናከር ነው የተያዘው። ይህ ማለት ወደ ፊት የዓለም ገበያ በአካባቢዎች የገበያ እንቀስቃሴ(Regional Blocks) ይወሰናል ማለት ነው።

        ይህ ሁኔታ ጉዳትም ጥቅምም አለው። ጉዳቱ ለጊዜውም ቢሆን የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀዘቅዝ ቢያደርግና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የስራ መስኮች ቢወድሙም፣ከረዢም ጊዜ አንፃር ግን የነጻ ገበያ አራማጅ ኢንስቲቱሽኖች፣ ለምሳሌ እንደ ዓለም ንግድ ድርጅት(WTO) ዐይነቱ እየተዳከሙና ሚናቸው እየቀነሰ ይመጣል። እንደሚታወቀው እስከዛሬ ድረስ ብዙ ሃገሮች፣ የሶስተኛውን ዓለም ሃገሮችንም ጨምሮ ተፈጥሮን የሚቀናቀን የአመራረት ስልትና የኃይልን(Energy) አጠቃቀም የሚያባብስና በተፈጥሮና በሰው ህይወት መሀከል ያለው ግኑኝነት እንዲናጋ የሚያደርግና ጤንነትን የሚያቃውስ ሂደት ነው የሚታየው። በዚህ ዐይነት የአመራረት ስልትና የኃይል አጠቃቀም ዘዴ በተለይም የሶስተኛው ዓለም ሃገሮች እየተጠቁና ብዙ ህዝቦችም ከቦታቸው እየተፈናቀሉና ጤናማ በሆነ መልክ ሊሰሩና ሊያርሱ የማይችሉበት ሁኔታ በተለይም ባለፈው ሰላሳ ዐመት ተፈጥሯል። በሌላ አነጋገር ባለፈው ሰላሳ ዐመት ዓለም በፍጆታ ምርት ብትሽብረቀረቅምና እኛም የአዳዲስ ቴክኖሎጀዎች ተጠቃሚ ብንሆንምና በኢንተርኔት አማካይነት ግኑኝነታችን ቢቃረብም፣ ይህ ሁሉ በከፍተኛ የጤንነት ቀውስ የተገኘ ውጤትና ተፈጥሮን ካለምንም ደንታ በመበዝበዝ የተደረሰበት የኑሮ ደስታ ነው። ከዚህ ስንነሳ ለጊዜውም ቢሆን በተፈጠረው ቀውስ መደናበር ቢፈጠረምና ወደ ሃገር ቤት የምንለከው የገንዘብ መጠን ቢቀንስም ከራሳችን ጤንነት አንፃር፣ ተፈጥሮን በስነ-ስርዓት ከመጠቀምና ለመጭው ትውልድ በጥሩ መልክ ከማስታላለፍ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር የዛሬው ቀውስ እንደ አደጋ ብቻ መታየት የለበትም። እንድናስብና አዳዲስ ስትራቴጂ እንድንቀይስ የሚገፋፋን መሆን አለበት። ከዚህም ስንነሳ የዛሬው የፋይናንስ ቀውስ የሚያሰተምረን እስከምን ድረስ መሄድ እንደምንችልና፣ ከመጠን በላይ የበላ ሰው መንቀሳቀስ እንደማይችል ሁሉ፣ ይህ ዕድገት የሚባለውም እየታሰበ የሚካሄድ ካልሆነ ራሷ ተፈጥሮ እንደምታምጽና በቀላሉ ልንቋቋመው የማንችለው ቀውስ ውስጥ ልንገባ እንደምንችል ነው የሚያስተምረን። በዚህ ዐይነቱ የማበጥና የመስፋፋት፣ እንዲሁም ሃገሮችን እያስገደዱ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ተቀባይ እንዲሆኑና ገበያቸውንም ክፍት እንዲያደርጉ ማስገደድ ለአሜረካንም ሆነ ለአውሮፓው የጋራ ገበያ ዋናው ስትራቴጂና የጥሬ.ሀብትን መቆጣጣሪያ ዘዴ ነበር። ይሁንና ግን ይህ እብጠት ደግሞ ወደ መፈንዳትና ዓለምን ወደ ማተረማመስ ላይ ደርሷል። በተለይም አሜሪካ በዚህም የማበጥና የመስፋፋት ስትራቴጂና እንዲሁም ደግሞ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ ኃይልና የበላይነት ዓለምን የሚቆጣጠር መስሎት ነበር።ተፈጥሮ ግን ከዚህ በላይ መሄድ አትችልም፤ጊዜህ አልፎብሃል እያለችውና ወደ ውስጥ ደግሞ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ኢኮሎጂያዊና ህብረተሰብአዊ ቀውስ እየደረሰበት ነው። የፈለገው ፓርቲም ስልጣንን ቢወስድ ወይም ቢመረጥ ይህንን ዐይነቱን ቀውስ ሊቆጣጠርና ስድሳ ዐመት ያህል የነበረውን የበላይነት እንደገና መልሶ ሊያጎናጽፈው በፍጹም አይችልም።

የርዕዮተ-ዓለም ቀውስ ወይስ የስርዓቱ ገጽታ !!

          እንደዚህ ዐይነቱ የፋይናንስ ቀውስ ከተከሰተና ቀስ በቀስም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚው እየተሸጋገረ ከመጣ ወዲህ፣ ራሳቸውን የኒዎ ሊበራል ኢኮኖሚ ምሁሮችንና ሙሉ በሙሉ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙትንና ሌላ አስተያየት ያላቸውንም ኤክስፐርቶች የሚነጋግረው ጉዳይ ቀውሱ የስርዓት ነው ወይስ የኒዎ-ሊበራሊዝም ርዕዮተ-ዓለም ጭፍን ፖሊሲ ውጤት ነው የሚል ነው። በተለይም ትችታዊ አመለካከት ያላቸው ስርዓቱ የፈጠረው ቀውስ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ስርዓቱ ሳይሆን ከመጠን በላይ የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣው የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም በመንግስትም ደረጃ ተቀባይነትን መቀዳጅቱና ኢንስቲቱሽናዊ ባህርይ ማግኘቱ ሲሆን፣ ሁሉም ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴ ወደ ትርፍነትና ወደ ኢኮኖሚያዊ ባህርይ በመወሰዱና ህዝቡን ግራ በማጋባቱ ነው የሚል ነው። ይህንን በመጠኑም ቢሆን እንመልከት።

         በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ያለው ችግር ካፒታሊዝም እንደተፈጥሮአዊና ሁሉም ነገር እንዳለ(assumed) ሆኖ በትምህርት ቤት መሰጠቱ ነው። ስለሆነም በትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ መጽሀፎች ካፒታሊዝም የታሪክና የህብረተሰቦች ግጭት ውጤትና ሄደት ሳይሆን የኖረና ወደ ፊትም የሚኖር ስርዓት ነው። በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው ውስጥ የሚሳተፉት ሁሉ እንደየ አስተዋጽዎአቸው ጥቅም ያገኛሉ። መሬት ያለውና የሚያከራይ፣ ለመሬቱ ኪራይ ያገኛል፤ ካፒታል ያለው ደግሞ ተግባራዊ ካደረገ ወለድ ያገኛል፤ ሰራተኛው ደግሞ ለጉልበቱ የሚመጣጠን ገቢ ያገኛል። በዚህም ምክንያት ሁሉም ተካፋዮች እንደየ አስተዋጽዎአቸው ጥቅም የሚያገኙና ከፍተኛውን ጥቅም(Maximum Profit or Utility) የሚያሳድዱ ናቸው ይላል። በሌላ አነጋገር፣ በዚህ ዐይነት ኢኮኖሚ ውስጥ ፓሬቶ የሚባለው ኢኮኖሚስት እንደሚለው፣ የአንዱ ጥቅም ማግኘት ሌላውን አይጎዳም። ይሁንና ግን በአራት መቶ የካፒታሊዝም ታሪክ ውስጥ የትምህርት ቤት አኮኖሚክስ መጽሀፍ እንደሚለን ሁሉም ተካፋዮች ተመሳሳይ የመደራደር መብት ያላቸው ሳይሆን፣ የፍጆታ አጠቃቀምና ገቢ(Income) እንዲሁም የስራ ሰዐት ቅነሳና በስራ ቦታ ጤንነትን መንከባከብ፣ ሰራተኛውም በተጠሪዎቹ አማካይነት የመደራደር ኃይል እያገኘ የመጣው ከብዙ ትግል በኋላ ነው። በዚህም ምክንያት፣ በምዕራቡ ዓለም ካፒታሊዝም እያደገና ከተስፋፋ በኋላ የግል ሀብትን በሚመለከት፣ በተለይም መሬትና ገንዘብ በጥቂት ሰዎችና ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው የመጡት። ስለሆነም የካፒታሊዝምን ዕድገት ወሳኞችና የምርት እንቅስቃሴ ደንጋጊዎች ካፒታሊስቶች እንጂ አብዛኛው ሰፊ ህዝብ አይደለም። እዚህ ላይ ነው በብዙ ግራፎች አሸብርቆ የሚታየው የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ይህንን ሀቅ ማሳየት የማይችለው። ከዚህ ስንነሳ የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ መጽህፍ በተለይም እኛን ከሶስተኛው ዓለም የመጣን ተማሪዎች ሀቁን እንዳናውቅ ጭንቅላታችንን ጋርዶታል ማለት ይቻላል።

          ወደ ስርዓቱ የውስጥ-ኃይል ስንመጣ፣ ብዙ ከታሪክ አንጻር የተጻፉ የኢኮኖሚክስ መጽሀፎችን ላገላበጠ፣ ካፒታሊዝም የበላይነትን ሊቀዳጅ የቻለው በመጀመሪያውኑ በመንግስት ቅድመ-ሁኔታዎች ከተመቻቹለትና ከዚህ በፊት ተብትበው ከያዙት የዘልማድ አስራር ቀስ በቀስና በጉልበትም ጭምር እየተላቀቀ ከመጣ በኋላ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚለን ሳይሆን፣ በካፒታሊዝም ዕድገት ውስጥ የመንግስት ሚናና አመጽ ከፍተኛ ቦታውን ይወስዳሉ ማለት ነው። በዚሀም መሰረት በታሪክ ውስጥ በተለያየ መልክ የታየው የመንግስት ስርዓት ራሱ ሀብት አሸጋሻጊ ኃይል እንደነበር ይታወቃል። ከተለያዩ የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ውስጥ ቀረጥና(Tax) ልዩ ልዩ የሀብት ማዳበሪያ ዘዴዎችና ጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ጠቃሚ መሳሪያዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ መጥተዋል። ስለሆነም ይህንን በሚመለከትና በካፒታሊዝም ዕድገት ውስጥ የተካሄደው የኃይል አሰላለፍ ለውጥና በየጊዜው ቀውስ መታየት የግዴታ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ብቅ እንዲሉ አስገድዷል። በተለይም በ1929 ዓ.ም ከታየው ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ(The Great Economic Deprssion) በታላቁ የእንግሊዝ ኢኮኖሚስት ኬይንስ የዳበረው የኢኮኖሚ መሳሪያ፣ ማክሮ ኢኮኖሚክስ እየተባለ የሚጠራው፣ በጊዜው የነበረውን በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የሚወከለውን ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ለምን እንደማይሰራና ካፒታሊዝም በአፈጣጠሩ ከፍና ዝቅ የሚልና ህብረተሰብንም ሊያመሰቃቅል እንደሚችል የሚያሳይ ትንተና ነው። ስለዚህም በኬይንስ አመለካከትና ዕምነት ካፐታሊዝም ቁጥጥር የሚያስፈልገውና በመንግስት ጣልቃ-ገብነት(Deficit Speneding) እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ሚዛኑን እንደሚጠብቅ ነው። ስለሆነም በመጀመሪያ በፕሬዚደንት ሩዝቬልት በ1930ዎቹ The New Deal ተብሎ በሚታወቀው ፖሊሲ አማካይነት ተግባራዊ የሆነው የመንግስት ጣልቃ-ገብነት፣ ሰፊውን ህዝብ በብድርና በደሞዝ ዕድገት ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ኢኮኖሚው ማንሰራራት ቻለ። ፎርድ መኪና መኪናን አይገዛም እንዳለው ሁሉ፣ በአዲሱ ኒው ዲል ፖሊሲ መሰረት አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም በተለይም አሜሪካ ውስጥ መስፋፋት ጀመረ። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነትም በኋላ በጦርነቱ የተከሰከሰው የአውሮፓ ኢኮኖሚ እንደገና ሊገነባ የቻለው ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስና በመንግስት ጣልቃ-ገብነት አማካይነት ነው። ይህም የሚያረጋግጠው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች አንደሚሉት የገበያ ኢኮኖሚ በራሱ ውስጣዊ ባህርይ ወይም መሳሪያዎች ራሱን የሚያርምና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሳይሆን በድርድርና በመንግስት ጣልቃ-ገብነት ነው ሊንቀሳቀስ የሚችልውና ዕድገትን የሚያመጣው። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት ካፒታሊዝም ካለመንግስት ጣልቃ-ገብነት በንጹህ መልክ የተከናወነበትና ያደገበት ወቅት አልነበረም። ፕሮፌሰር ካርል ፖላኒ „The Great Transformation“ በሚለው ግሩም መጽሀፋቸው ውስጥ እንዳረጋገጡት፣ እንግሊዝ ሃገር ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ላይ ተሞክሮ ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ቀውስ ስላስከተለ የግዴታ መንግስት ጣልቃ መግባት እንደተገደደ ያረጋግጣሉ።

         ስለዚህም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ አራማጆች ስርዓቱን ወደ ንጹህ ርዕዮተ-ዓለም እንዲለወጥ በማድረግና በመንግስትና በሌሎች ኢንስቲቲሽኖች ላይ የበላይነትን በመቀዳጀት የካፒታሊዝምን ሂደት ማጣመም ተያያዙ። ይህ የርዕዮተ-ዓለም ሰበካና ውስጥ ካለው ባህርይ ጋር ተደምሮ መንግስትን ሙሉ በሙሉ የጠቅላላው ህብረተሰብ ሳይሆን የጥቂት ባለሀብቶች ሀብት ማሸጋሸጊያ መሳሪያ በማድረግ እንዲያውም እነሱ ሚዛናዊ ነው ብለው የሚሰብኩት ትምህርትና ስራዓት ሚዛኑን እያጣ እንዲመጣ አደረጉት። በከፍተኛ ደረጃም ሀብት እየተሸጋሸገ ወደ ተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል እጅ ዘንድ እየተከማቸ መጣ። ይህ ሁኔታና ሰበካ እንዲሁም ደግሞ ስር እየሰደደ የመጣው የተዛባ አመለካከት  ስግብግብነትንና በጥቂት ትርፍ ብቻ አለመርካትን አስከተለ። በብዛት ገንዘብ ያለው ብዙ ትርፍ ለማግኘት ሲል ሀብቱን ወደ ቁማር ጨዋታ ላይ ማስቀመጥ ወይም ደግሞ ቀረጥ ላለመክፈል ሲል በባንኮች ዕርዳታ ገንዘቡን ከሃገር ውስጥ ማሸሽና ቀረጥ ወደ ማይከፈልባቸው ደሴቶችና ሃገሮች ማስቀመጥ ጀመረ። ባንኮች ደግሞ የተፈጠረውን ከፍተኛ ወድድርና የመንግስት ፈቃድ ተገን በማድረግ ከፍተኛ ትርፍ ማትረፍ ያስፈልጋል በሚል- ለምሳሌ የጀርመን ባንክ ኃላፊ ቢያንስ 25% ትርፍ መገኘት አለበት እያለ ሰራተኞችን ያስጨንቅ ነበር- ወደ ተወሳሰቡና ግልጽ ወዳልሆኑ ያሰራር ዘዴዎች ተሸጋገሩ። ለዚህ ደግሞ ልዩ ልዩ የማጭበርበሪያ የፋይናንስ መሳሪዎች መፈጠር አለባቸው ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ ስግብግብነትና ሰራቶችን ማሰጨነቅ፣ እንዲሁም ደግሞ ትርፍም እያገኙ ብዙ ዐመት የሰሩ ሰራተኞችን ከስራ ማባረር የስርዓቱ ባህርይ እየሆነ መጣ። የድርሻ ክፍያ(Share Holder Value) ዋናው መለኪያና ርዕዮተ-ዓለም ሆነ ማለት ነው።

        የዚህ ዓይነት የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም መስፋፋትና ወደ ሶስተኛው ዓለም ሃገሮችም መዳረስ የህዝቦችን አኗኗር ብቻ ሳይሆን ግንኝነታቸውንና የከተማ አገነባቦችን በመቀየር ህብረተሰቦችን ማዘበራረቅ ጀመረ። በተለይም ቻይናና አንዳንድ የሩቅ ምስራቅ ሃገሮች በዚህ ዐይነቱ ርዕዮተ-ዓለም ከተጠመዱ በኋላ የገበያ ቦታዎችም ሆነ የከተማ አገነባቦች ከተፈጥሮ ውበት ጋር እየተቀናጁና የህዝብን ጤንነት ግምት ውስጥ በማስገባት መገንባት ሲገባቸው ወደ ንጹህ ገበያነትና ትርፍ አምጭነት በመቀየር ሰውን ማንቀዥቀዥ ጀመሩ። ከተማዎች ጤናማ መወዳደሪያ ቦታዎች መሆናቸው ቀርቶ ገንዘብና ጉልበት ያለው እንዲሁም ደግሞ ከአንዳንድ ባለስልጣናት ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያላቸው እንደልብ የሚዋኙበት ሆነ። ከተማዎች፣ ጥቂቶቶች ባለሀብቶች ደካማውን የሚገፉበትና የፈለጉትን ዐይነት ህንፃ የሚሰሩበት መድረክ ሆኑ። እንደዚህ ዐይነቱ የህንጻ አስራር ደግሞ በጣም የሚያሰፈራ ከመሆኑና ግለሰበኝነትም እየተስፋፋ በመምጣቱ ብዞዎች መቋቋም ሲያቅታቸው ራሳቸውን ማጥፋት ተያያዙ። ለምሳሌ ቻይና ውስጥ ከኢንዱስትሪ ቆሻሻ ከሚወጣው ቀጥሎና በሰው ህይወት ላይ አደጋ ከሚያደርሰው የጤንነት መቃውስ ቀጥሎ የግለሰቦች ራሰን መግደል በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣት ነው። በኢንዱስትሪ ሃገሮችም ያለው ችግር ይህ ነው። ከ1980ዎቹ ጀምሮ እየተሰሩ የመጡት በመስታወት ያሸበረቁ ትላልቅ ህንፃዎች ሰፊውን ህዝብ ተራ የፍጆታ ተጠቃሚ ከማድረግ አልፈው የማሰብ ኃይሉን እየመረዙትና አመጸኛም እንዲሆን እያደረጉት ነው። በተጨማሪም ዕውነትንና ውሸትን ለማመዛዘን የማይችል እየሆነ የመጣ ነው። ይህ ዐይነቱ ልቅ የገበያ ኢኮኖሚና የፍጆታ አጠቃቀም፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሚብለጨለጩ እቃዎችን ገዝቶ ለመጠቀም አለመቻል ነፍሰ ገዳዮችንና ዘራፊዎችን እየፈጠረ ነው። ህብረተሰቦች እየተዘባረረቁና ከመንፈሳዊነት ይልቅ ማቴሪያሊስትነት እየተስፋፋ ነው። ሁለቱም ሊጣጣሙ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ወደኛ ሃገርም በመዛመቱ፣ ባለፉት አስራ ስምንት ዐመታት ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትና የፍጆታ አጠቃቀም በመፈጠር የህዝባችንም ባህርይ ከሰውና ከገንዘብ ጋር ያለው ግኑኘነት ወደ መጥፎ አቅጣጫ እያመራ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። ገንዘብና ሀብታም መሆን ዋናው የህብረተሰብአዊ ግኑኝነት መለኪያዎች ሆኑ።

         ይህንን ትተን ሌሎች ለኛ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ የቲዎሪና የፍልስፍና ጥያቄዎችን ሳላነሳና ትንተና ውስጥ ሳልገባ፣ በታሪክ ውስጥ ካፒታሊዝም ውስጠ-ኃይል ያለው ስርዓት ነው። በመጀመሪያ ግን በታሪክ እንደተረጋገጠው፣ ለካፒታሊዝም ቅድመ-ሁኔታዎች የተነጠፉት በፊዩዳሉ ስርዓት ውስጥ ሲሆን፣ የቤተክርስቲያን ቀሳውስትና የተገለጸላቸው㔫ነጋዴዎች ለከተማዎችና ለካቴድራሎች ግንባታ፣ ለገበያ አዳራሾች መቆርቆርና ለዕደ-ጥበብ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽዎ አድርገዋል። በዚህ ዐይነት ስርዓት ውስጥ ነው የኋላ ኋላ ካፒታሊዝም የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣው። ያም ሆነ ይህ፣ በዚህ ዐይነት መልክ እያደገና እየተስፋፋ በመጣ  ስርዓት ብቻ ነው ዛሬ የምናየው የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊታይ የቻለው። በሌላ አነጋገር፣ ለካፒታሊዝም ማደግ ቢያንስ ስድስት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት አለባቸው። የመጀመሪያውና ዋናው የካፒታሊዝም አንቀሳቃሽ ኃይል የሰዎች አስተሳሰብ መለወጥ ነው። ህብረተሰቦች በዘልማድ ከሚሰሩበትና ከሚኖሩበት ሁኔታ ሲላቀቁና ተፈጥሮና ባህል ከጫነባቸው ጭነት እየተላቀቁ ሲመጡ ራሳቸውን ማሸነፍና አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር ቻሉ። ለዚህ ደግሞ የግሪኩ ስልጣኔና የኢጣሊያኑ ሬናሳ ለካፒታሊዝም ወይም ለከበርቴው ራሽናሊቲ ከፍተኛ አስተዋጽዎ አድርገዋል። አስተሳሰባቸውን በዚህ መልክ ማደስ ያልቻሉና የአኗኗር ስልታቸውን ያልቀየሩ ህብረተሰቦች ግን እዚያ በዚያው እየዳሸቁ እንዲኖሩ ተገደዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የግል ሀብት ቀስ በቀስ በኢንስቲቱሽን ደረጃ መረጋገጡና ህጋዊ መሆኑ ለካፒታሊዝም ዕደገት ዋናው መሰረት ሆኗል። በሶስተኛ ደረጃ፣ አዲስ የራሱን ጉልበት እየሸጠ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ማለት ለካፒታልዝም ዕድገት የማይታበል አስተዋጽዎ አድርጓል። በአራተኛ ደረጃ፣ ግልጽ  የሆነ የስራ ክፍፍል መዳበርና በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል ግኑኝነት መፈጠርና መተሳሰር ለካፒታሊዝም ዕምርታ ሰጥቶታል። አምስተኛ፣ የባንኮች ማደግና አበዳሪ መሆን የዕቃን መሽከርከርና የንግድ ልውውጥን አፋጥኗል። ስድስተኛ፣ አዲስ ዲይናሚክ የከበርቴ መደብ በመፈጠር ካፒታሊዝም ሁለንታዊ ኃይል እንዲኖረው ለማድረግ ችሏል። አሁን ያለው ክርክር እንደዚህ ዐይነቱን ስርዓት በሌላ መተካት ይችላል ወይስ ስርዓቱን መቆጣጠር ይቻላል ብሎ አማራጭ ማቅረብ ሳይሆን፣ የኒዎ-ሊበራሎችን የበላይነት ተቋቁሞና አሸንፎ ካፒታሊዝምን ሰብአዊ በማድረግ ከገባበት ቀውስ ውስጥ ማውጣት ይቻላል ወይ ? የሚለው ነው የሚያከራክረው።

           በእኔ ዕምነት እስከተወሰነ ደረጃም ቢሆን ህዝቦች ህልማቸውን ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉት በካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ ብቻ ነው። የካፒታሊዝም ዕድገትም ሊታይ የሚችለው ውድድር ሲኖር ብቻ ነው። ህብረተሰቦችን በሌላ መልክ ማደራጀት የሚያስቸግር ይመስለኛል። የሚነሳው ጥያቄ ስርዓቱን እንዴት አድርጎ መቆጣጠር ይቻላል የሚል ነው። ይህ ሊወሰን የሚችለው የህዝቦች የማሰብ ኃይል የዳበረ እንደሆነና በየጊዜው በሚፈልቅ የተበላሸ ርዕዮተ-ዓለም ያልተመረዘ እንደሆን ብቻ ነው። የተበላሹ አመለካከቶችን ደግሞ ሙሉ በሙሉ መቋቋም አይቻልም። ለምን እንደሆን አይገባኝም ሰዎች ጥሩውንና ቀናውን መንገድ ከመከተል ይልቅ ወደሚያጠፋቸው ያዘነብላሉ። ያም ሆነ ይህ ከዚህ እጅግ እስቸጋሪ ሁኔታ ስነነሳ ዛሬ በኢንዱስትሪ ሃገሮች የፋይናንስ ገበያውን ለመቆጣጠር የሚወጡት ህጎች ስርዓቱን መልክ ሊሰጡት ይችላሉ ወይ ? እስከምንስ ድረስ ሊሰራ ይችላል?

የፋይናንስ ገበያውን ለማስተካከል ሊወሰዱ የታቀዱ እርምጃዎች !!

          ከሁለት ዐመት በፊት እንደዚህ ዐይነቱ አደጋ ሊከስት ይችላል ብለው፣ በተለይም ደግሞ የኢንቬስትሜንት ባንኮች የበላይነትና ኢንዱስትሪዎችን እየገዙ የተወሰነውን ክፍል አውድሞ ትርፍ ማካበት ያሳሰባቸው እንደ ጀርመን ያሉ መንግስታት የፋይናንስ ገበያው እንዲታረም ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም በእንግሊዝና በአሜሪካን መንግስት ከፍተኛ ተቃውም ሊገታ ችሏል። እ.አ በ1998 ዓ.ም በጊዜው የጀርመን ፋይናንስ ሚኒስተር የነበሩት ሚስተር ላፎንቴ የካፒታል እንቅስቃሴ እንዲታገድና የፊዴራሉን ባንክ ሚና ከመንግስት ፖሊሲ ጋር መጣጣም አለበት ብለው ሙከራ ሲያደረጉ የአሜሪካና የእንግሊዝ ጋዜጦችም ሆነ መጽሄቶች „በጣም አደገኛው የአውሮፓ ሰው“ በሚል በሰውየው ህይወት ላይ የተቃጣ ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ። ሚስተር ላፎንቴም ይህንን ጭነት በመፍራትና የሽሩደር መንግሰት መልፈስፈስ ሲጀምርና የገባውን ቃል ኪዳን ሲሽር ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተገደዱ። በጊዜው ሚሰተር ላፎንቴ በሶሻል ዲሞክራት ጓደኞቻቸው የሚሳቅባቸውና የሚጮሁባቸው ሆኑ። ሰውየው ግን ባላቸው የምሁር ጥንካሬና ብስለት እንደገና አዲስ ፓርቲ መስርተው በማንሰራራት ለራሱ ለሶሻል ዶሞክራቲክ ፓርቲ የራስ ምታት ሆኑበት። በዚያን ጊዜ የተናገሩት ሁሉ ስለደረስ ዛሬ የሚፈሩ ናቸው። አሁን ይህ ቀውስ ከተከሰተና ገበያውን ማምታታት ከጀመረ ወዲህ የካፒታል ገበያውን በአዲስ መልክ ማሰተካከል አለብን እየተባለ ከሚስተር ሳርኮሲንም ሆነ ከጀርመን መንግስት፣ በተለይም ከፋይናንስ ሚኒስተሩ የሚቀርበው ውትወታና እርማት የቱን ያህል የካፒታል ገበያውን ሊያስተካክል ይችላል ? እስከምንስ ድረስ መተማመንን ሊፈጥር ይችላል ? የሶስተኛው ዓለም ሃገሮችስ የዚህ አዲስ የፋይናንስ አርክቴክቸር ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላል ወይ ? የአሜሪካንስ ሚና ምን ይሆናል ?  እነዚህን ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ለመመለስ እንሞክር።

        እንደሚታወቀው እ.አ በ1971 ዓ.ም የብሬተንስ ውድስ( Brettons-Woods)ስምምነት ከፈረሰና በ1973 ዓ.ም ደግሞ ተለዋዋጭ ገንዘብ(Variable Exchange Rate System) ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ የካፒታል ገበያው በአዲስ መልክ ተደራጀ። ዶላር ከወርቅ ጋር ያለው ግኑኝነት ቢላቀቅምና አሜሪካንም በተለይም በውጭ ኢኮኖሚው እየተዳከመ ቢመጣም አሁንም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋናው የሀብት ማከማቻና የንግድ መገበያያ ገንዘብ የአሜሪካ ዶላር ነው። ሆኖም ግን፣ በአንድ በኩል ከውስጥና ከውጭ  ኤኮኖሚው መዳከም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ተጨባጭ ኢኮኖሚው ከሚችለው በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሽከረከረው ጥሬ ገንዘብ አደገኛ ሁኔታን እየፈጠረ ነው። ዶላር በእምነት፣ በሚሊተሪና በፖለቲካ የሚደገፍ ከመሆኑ በስተቀር በተጨባጭ ኢኮኖሚ ወይም በወርቅ የሚደገፍ አይደለም። ይህም ማለት የአሜሪካ ኢኮኖሚ ቢንኮታኮትና የዶላርም የመግዛት ኃይል እየተዳከመ ከመጣ ሀብታቸውን በዶላር ያስቀመጡ ሃገሮችም ሆነ ግለሰቦች በአንድ ጊዜ ሊወድም ይችላል ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት የዶላር ሚና በጥያቄ ውስጥ መግባት ከጀመረ ወደ ሃያ ዐመት ሊጠጋው ነው። ይሁንና ይህንን ደፍሮ የሚያነሱ መንግስታት ሳይሆኑ ሰፋ ያለ ዕውቀት ያላቸው ከሜይን ስትሪም ውጭ ጥናት የሚያቀርቡ ምሁሮች ናቸው። ነገሩ ግን ወደ ውጭ እየወጣ የሚያነጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ከዚህ በመነሳት በወርቅ የተደገፈ ገንዘብ ወይም ደግሞ የተለያዩ ጠንካራ ከረንሲዎች የሚሳተፉበት(Currency Basket)ወይም ደግሞ ጎን ለጎን ሁለትና ሶስት ጠንካራ ገንዘቦች ዓለም አቀፋዊ የመገበያያና ሀብት የማከማቻ ገንዘቦች እንዲሆኑ ለውይይት እየቀረበ ነው። ይህንን ሃሳብ ለጊዜውም ቢሆን አሜሪካ ሊቀበለው አይፈልግም።

         ከዚህ ስንነሳ በኢንዱስትሪ ሃገሮች የፋይናንስ ገበያውን ለማረምና ለመቆጣጠር የሚወሰደው ርምጃ የተሟላ አይሆንም።  አሰራሩ ግልጽ መሆን አለበት የሚለው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። እንደምናየው እርማት ወይም፣ ማስተካከያ የሚያወጡ በገበያው ሲጠቀሙ የነበሩ ማኔጀሮች ናቸው። ለምሳሌ የአሜሪካ የፊናንስ ሚኒስተር የዎል ስትሪት ሰው የነበሩና በጊዜው በጣም ትልቁ የሚባለው የጎልድ ማን ሳክስ ዋና ኃላፊ የነበሩ ሰው ናቸው። እኚህ ሰውም ሆኑ ከበታች ያሉ ሰራተኞቻቸው በምንም ዐይነት የዎል ስትሪት ሰዎችን የሚጎዳ ህግና ቁጥጥር አያወጡም። ስርዓቱን ለመቆጣጠር ተብሎ ከተመደበው 700 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ዎል ስትሪት ሰዎች ፈሷል። ሁለተኛ፣ የኢንዱስትሩ ሃገሮች ጠቅላላውን ስርዓት ሳይነኩ ትንሽ በለሰለሰ መልክ ካሻሻሉ በኋላ የፋይናንስ ገበያው በድሮው መልኩ እንዲቀጥል ሳይወዱ በግድ ይገፉበታል። ከዚህ አልፈው ግን ስርዓቱን ጥያቄ ውስጥ ማስቀመጥና የማኔጀሮችን ሚና ማዳከም ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን የኢኮኖሚ የበላይነት እንደማዳከም ይቆጠራል። ስለዚህም ይህ ዐይነቱ ልፈፋ የወረቀት ነብር  ዐይነት እንጂ ወደ ሌላ ሊያልፍ የሚችል አይደለም። ከዚህ በላይ ደግሞ፣ ከላይ እንደተዘረዘረው እጅግ እየተወሳሰበ የመጣው ከአብዛኛው ህዝብ ገንዘብ መጣጭ የሆነው የተለያዩ የኢንሹራስ ውሎችና ፖሊሲዎች ናቸው። ለምሳሌ ከጤንነትና ከመኪናና ከአንዳንድ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ውሎች በስተቀር አብዛኛዎች የሰራተኛውን ንጹህ ገቢ የሚጋሩና ራሱ ሰራተኛው ሀብት እንዳያፈራ የሚያግዱ መንገዶች ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀረጥና በሌሎች አማካይነት ለሀብታሞች የሚፈሰውና በደሀና በሀብታም መሀከል ልዩነት እንዲሰፋ የሚያደርገው የኢኮኖሚ መሳሪያዎች በሙሉ ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። እነዚህን ትተን በካፒታል ገበያ ላይ የሚሽከርከሩ ወይም ደግሞ መገበያያ የሆኑ መሳሪያዎች እንዲቆሙ የሚያደርጉ አይደሉም። ለምሳሌ ዴሪቫቲቭና አሁን የፋይናንስ ገበያውን ቀውስ ውስጥ የከተተው ሰርተፊኬት በመባል የሚታወቀው ማጭበርበሪያ መሳሪያና ድርሻ(Stock) ሳይኖር መሸጥና መወራረድ(Empty Trade) እነዚህ መከልከል ያለባቸው ናቸው። በተጨማሪም በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ውስጥ ያሉ የኢንቬስትሜንትና የሄጅ ፈንድስ ቢሮዎች ወይም ገንዘብ ማሸሻዎች ሊዘጉ አይችሉም። እንግሊዝና አሜሪካን ይህንን በፍጹም አይፈቅዱም። ነገሩ በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም።

           ከዚህ ውጭ የሚነሳው ጥያቄ በተለይም የሶስተኛው ዓለም ሃገሮች ሚና ነው። ከሰላሳ ዐመት በላይ በመጀመሪያ በቀድሞው የጀርመኑ ካንሰለር በሚስተር ዊሊ ብራንድ የተነሳውና ሲያታግል የነበረው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስተካከለ የንግድ ልውውጥና የሀብት መሸጋሸሸግ አሁንም እየተነሳና እያነጋገረ ነው። የብዙ የሶስተኛው ዓለም ሃገሮች ሁኔታ በዚህ ይቀጥላል ወይስ አንድ የተስተካከለ የንግድ ልውውጥና የስራ ክፍፍል ሁኔታ ይፈጠራል ወይ ነው። በተለይም እስካሁን ድረስ የሰፈነው ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ በህብረተሰቦችና በአካባቢዎች ላይ ያመጣውን ተጽዕኖና አደጋ የሚቃወሙ የግዴታ የዓለም ንግድ መስተካከል እንዳለበትና፣ የሶስተኛው ዓለም ሃገሮችም ተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠር እያሉ በማሳሰብ ነው። ከዚህ ቀደም ብለው የሚሄዱ ደግሞ አሉ። የካፒታሊስት ኢኮኖሚም ሆነ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ በዚህ መልክ ሊቀጥል እንደማይችል፣ በተለይም የሶስተኛው ዓለም ሃገሮች ገቢያዎቻቸውን ልቅ ማድረግ የለባቸውም፤ ከተፈጥሮ ጋር የማይጋጭ ብቻ ሳይሆን ሰፊውን ህብረተሰብ ሊያሳትፍ የሚችል የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ ፖሊሲ መከተል አለባቸው የሚል ነው። ብዙ የሚያወያዩ ነገሮች አሉ ማለት ነው። አስተሳሰቦቹ ሰፊና መጠናት ያለባቸው ናቸው።

          ይህንን ትተን ከሃምሳ ዓመታት በላይ ዓለምን ሲቆጣጠሩ የነበሩ ኢንስቲቱሽኖች ሚና ነው። ብዙ ትችታዊ አመለካከት ያላቸው፣ አይ ኤም ኤፍ፣ የዓለም ባንክና የዓለም ንግድ ድርጅት የካፒታሊስት ሃገሮችን ጥቅም የሚያስጠብቁና ለብዙ የሶስተኛው ዓለም ሃገሮች ኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ ናቸው ሲሉ፣ ድርጊታቸውም መገታት እንዳለበት ያሳስባሉ። የሰሩትንም ወንጀል በብዙ መቶ መጽሀፎችና መጽሄቶች እያጠኑ አቅርበዋል። ስለዚህም አይ እነዚህ ኢንስቲቱሽኖች ሪፎርም መደረግ አለባቸው፤ ካለዚያም መውደም አለባቸው የሚሉ አሉ። ስለዚህም፣ ስለ ዓለም ገበያ ንግድና ስለፋይናንስ ገበያው መስተካከል በሚወራበት ጊዜ ሁኔታዎች በድሮ መልካቸው መቀጠል እንደሌለባቸው ትግል እየተደረገ ነው። በተለይም እንደ ቻይናና ብራዚል አበዳሪና ዓለም አቀፍ ተዋናይ እየሆኑ በመጡበት ወቅት፣ የእነ አይ ኤም ኤፍና ዓለም ባንክ ሚና ትርጉም እያጣ መጥቷል። ስለዚህም የግዴታ የእነዚህ ድርጅቶች በየሃገሩ እየገቡ መፈትፈትና ህብረተሰቦችን የማናጋቱ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል የሚሉና የሚታገሉ አሉ።

         ያም ሆነ ይህ አዲስ የተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የኃይል አሰላለፍ እንደነ አሜሪካና ኢንስቱቲሽኖቻቸው የመሳሰሉት በዚህ መልክ ሊቀጥሉ እንዳይችሉ ያስገድዳቸዋል። አሜሪካ የፈለገውን ያህል እንቅፋት ልፍጠር ብሎ ቢያንገራግርም የገባበት የኢኮኖሚ ማጥ ቀላል አይደለም። ቻይናዎች ብቻ በአሜሪካ ገበያ ላይ ወደ 500 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አፍሰዋል። አሜሪካ በውጭ ንግዱ ተወዳዳሪ ሊሆን የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥረውበታል። ስለዚህም በዐመት ወደ 800 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ኪሳራ አለበት ወይም ደግሞ ወደ ውጭ ከሚልከው ወደ ውስጥ የሚገባው ከላይ በሰፈረው መጠን ይበልጣል ማለት ነው። ሰለዚህ በየቀኑ 3 ቢለዮን የሚጠጋ ገንዘብ ወይም ካፒታል ከውጭ ማምጣት አለበት። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ደግሞ ብዙ ስትራቴጂክ መስኮች  በቻይናዎች፣ በአረቦችና በራሺያ ኦሊጋርኪዎች እየተያዘና እየተቦረቦረ ነው። በሚቀጥለው ሃያ ዐመት ደግሞ እየጎላ በመጣው የዲሞግራፊ ለውጥ የአሜሪካ ሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰና የዓለምን ገበያ እንደፈለገው ሊያሽከረክርበት የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው። የአሜሪካ ዘመን(Pax America) ወደ ማለቅ እየተቃረበ ነው። ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው ። ኢምፓየሮች ካላወቁበት፣ ዓለምን እንደፈለግን ማከረባበት እንችላለን የሚሉ ከሆነና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልን የሚያስከትሉ ከሆነ በራሳቸው እብጠት ይፈነዳሉ። ከሮማውያን ኢምፓየር የምንማረው ሀቅ ይህንን ነው።

         እኛ ኢትዮጵያውያኖች ይህንን ሁኔታ እንዴት እንደምንከታተልና እንደምንገነዘብ ማወቅ አልተቻለም። እስካሁን ድረስ እንደምከታተለው የጆሮ ዳባ ብለን ተቀምጠናል።እኛን የማይመለከቱንና ከዓለም ኢኮኖሚና የፖለቲካ ክንውን ውስጥ እንደሌለን ነው የሚሰማኝ። የኢትዮጵያን ሁኔታ ደግሞ በተወሰነ መነጽር ብቻ የምንመለከት ከሆነ ትላልቅ ነገሮችን ለመስራት አንችልም። በራሳችንና በጠባብ ክልል ብቻ ልንወሰን አንችልም። በሌላ በኩል ደገሞ ታጋዮች ነን የሚሉ ቲአትር ከመስራት በስተቀር ሰፊው ወጣት ንቃተ-ህሊናው እንዲዳብር የሚያደርጉት አስተዋጽዎ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህ ዐይነት የትግል ስልት ከቀጠልናና ባለን ሚዲያ እየተጠቀምን ሃሳቦች እንዳይሰራጩ ተንኮል የምንሸርብ ከሆነ ሃገራችን ውስጥ ከተቀመጠው መንግስት የተሻለ ስራ አንሰራም ማለት ነው። ስለዚህ ግልጽና ትምህርታዊ ጽሁፎች ወደ ውጭ ወጥተው ሰፊ ውይይት እንዲካሄድባቸው ያስፈልጋል። ሃሳቦች መገደብ የለባቸውም ወይንም ደግሞ የወጣቱን ጭንቅላት የሚበርዙና  በጥልቀት እንዳይመለከት የሚያደርጉ ጽሁፎች ከመሰራጨት መቆም አለባቸው። በተጨማሪም ሰፊውን ወጣትና የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተማር የምንፈልግ ከሆናና ለሃገራችንም የምንታገል ከሆነ ቢያንስ ከሁለት አንድ ጽሁፍ በአማርኛ እየተጻፈ መቅረብ አለበት። በዚህ ዐይነት የትግል ዘዴና አስተዋጽዎ ብቻ ነው ታሪክ መስራት የምንችለው። መልካም ንባብ !!

 

                                                                                  fekadubekele@gmx.de

                                          

 

    

 

 

 

 

Â