[gtranslate]

ጦርነቱ የአፍሪካውያን  ሳይሆን የአሜሪካና የአውሮፓ ጦርነት ነው !

           ሻለቃ ዳዊት በቅርቡ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ስለሚካሄደው ጦርነትና

       ስለ  ኢኮኖሚ ዕድገት ለሰጠው ሀተታ መልስ

                                                                                   ፈቃዱ በቀለ (/)                                                                                         

                                                                                                                                     መጋቢት 31 2020

መግቢያ

ሻለቃ ዳዊት ብቻ ሳይሆን እንደሱ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው ምሁራን በተለያየ ወቅት የዓለም አቀፍንም  ሆነ የአገራችንን ፖለቲካ በሚመለከት በጽሁፍ መልክ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። በአቀራረባቸውም አንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳቡና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውን ናቸው እስከማለት አድርሷቸዋል። ይሁንና አንባቢው እነዚህ ምሁራን የሚሰጡትን አስተያየትና ሀተታ ለመረዳት የፍልስፍናቸውን፣ የቲዎሪዎቻቸውንና የሳይንሳቸውን መሰረት ይጠይቅ አይጠይቅ እንደሆን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አንዳንድ ጽሁፎች በጥሩ የእንግሊዘኛም ሆነ የአማርኛ ቋንቋ ተጠናቅረው በሚቀርቡበት ጊዜ አንባቢው የይዘታቸውንና የሀተታዎችን የኢንፎርሜሼን ምንጭ ሳይመረምር ዝም ብሎ በመቀበል ትክክል  ናቸው ብሎ ይደመድማል። እንደምከታተለው ከሆነ አብዛኛዎቹ አንባቢዎች እንደዚህ ዐይነቱን የሻለቃ ዳዊትን የመሳሰሉ ጽሁፎች ውስጣዊ ይዘት ለመመርመርና በተመሳሳይ አርዕስት ላይ ከሚጽፉ፣ ይሁንና ደግሞ በተለየ መልክ ከሚያቀርቡ ሰዎች ጋር የማወዳደር ጊዜና ገት ስለሌላቸው ከአንድ ወገን ብቻ የሚመጣውን ኢንፎርሜሽን አንብበው ትክክል ነው ብለው በመቀበል አላስፈላጊ ድምደማ ላይ ይደርሳሉ።

እንደምንከታተለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንፎርሜሽኖች በየደቂቃውና በየሰዓታቱ ይወጣሉ። እንደዚሁም በየቀናትና በየወራቱ ሰፋ ያሉ ሀተታዎች ይቀርባሉ። አብዛኛዎቹ በግልጽ የምናያቸውና የምናነባቸው ኢንፎርሜሽኖች ግን የተወሰነ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቁና፣ አብዛኛዎችም ዕውነት ያልሆኑ ወይንም ደግሞ በትንሹ „ዕውነትን“ ያዘሉ ናቸው። የሚንጸባረቁትም ኢንፎርሜሽኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሰንሰለት ርዕይ የሚያስተጋቡና ሌሎችን ይህንን እየተጻረሩ  የሚቀርቡ ሀተታዎችን የኮንስፒራሲ አቀራረቦች ናቸው በማለት የሚያጥላሉ ናቸው። እንደዚህ ዓይነቱ የሰውን ጭንቅላት ለመያዝና በአንድ የታሪክ ውቅት የተዘረጋን የአገዛዝ ሰንሰለትና ርዕዮተ-ዓለምን ሰፊ ህዝብ ትክክል  ነው ብሎ እንዲያምን ለማድረግ ፕሮፖጋንዳ መንዛት የተጀመረው ከሶስት ሺህ ዓመት ጀምሮ ነው። በታሪክ ውስጥ በተለያየ ኤፖክ የበላይነትን የተቀዳጁ ኃይሎች አይ በሰበካ ካሊያም በጉልብት በማሳመን የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም የሞከሩበት ጊዜ በታሪክ ማህደር ውስጥ በሰፊው ተመዝግቧል። በተለይም ከ6ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነትን በተቀዳጀበት ዘመን ሌሎች ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት ያላቸውን አስተሳሰቦችም ሆነ ሀተታዎች እንዳይራቡ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግ እንደነበረና፣ ይህንን የጣሱ ምሁራን እንደሚቃጠሉና ወደ እስርቤትም እንደሚከተቱ የታወቀ ጉዳይ ነበር።  ይሁንና ግን  የተቀሩት ኃይሎች በጊዜው ይደረግባቸው የነበረውን ጫናና ክትትል ባለመፍራትና ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር ለሀቀኛው መንገድ በመታገላቸው የካቶሊክን የርዕዮተ-ዓለም የበላይነት በመስበር የሳይንስ ጮራን በማንፀባረቅ ይኸው ሁላችንም የዘመኑ ስልጣኔ ባላቤቶችና ተጠቃሚዎች ለመሆን በቅተናል። በዚያን ዘመንና በኋላም ጭፍን ዕምነት ሳይሆን በምርምር ላይ የተመሰረተ ሳይንሳዊ ግኝት ተግባራዊ እንዲሆን እልክ አስጨራሽ ትግል ባይደረግ ኖሮ የሰው ልጅ ለብዙ መቶ ዐመታት በጨለማ ዓለም ውስጥ ሊኖር እንደሚችል መገመቱ ከባድ አይደለም። በዘመናችንም እንደ ጁሊያን አሳንጅ የመሰለው ኢንቬስቲጋቲቭ ጋዘጠኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምሁር ለህይወቱ ሳይፈራ ሲአይ ኤና  ፔንታጎን እንዲሁም የእንግሊዙ የስለላ ድርጅት የፈጸሙትንና የሚፈጽሙትን አሰቃቂ ወንጀሎች ጉዳቸውን ባያወጣና ለዓለም ህዝብ ባያሳውቅ ኖር  ከዚያ በላይ ሌላ ወንጀል ሊሰሩ ይችሉ ነበር። በዚህ ዐይነቱ ደፋርና ሰብአዊ ተግባሩ ክትትል ስለሚደረግበትና ገና የምሰራው ብዙ ስራ አለ ብሎ በማሰቡ ከሶስት ዓመት በላይ ለንደን የሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ከጸሀይ ተገልሎ መሽጎ ይኖራል ። ኤድዋርድ ስኖውደንም በውሸት ፕሮፖጋንዳ ከምታለል ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ ብሎ ለህሊናው ብቻ በመገዛት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶኩሜንቶችን ይዞ በመውጣትና ለጋዜጠኞች በመስጠት የሲአይ ኤንና የፔንታጎንን ርኩስ ተግባር እንድናውቀው ማድረጉ የዚህ ዐይነቱ የኢንፎርሚሽንን የበላይነት የማግኘት አንደኛው ትግል ነው።

በዛሬውም ወቅት ይህንን የመሰለውን የኢንፎርሜሽን የበላይነት ለመቀዳጀትና  ዘለዓለማዊ ለማድረግ አሜሪካንና ግብረአበሮቹ  የማያሰራጩት የውሸት ፕርፖጋንዳ የለም። እነሱ ከደሙ ንጹህ እንደሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ውዝግብና ጦርነት ወይም የህዝቦች መፈናቀል እጃቸው እንደሌለብት፣ ሲጠየቁ ብቻ ሄደው ሁኔታውን ገብ ለማድረግ እንደሚጥሩ ነው የዋሁን የዓለም ህዝብ ለማሳመን የሚሞክሩት። ከዚህ ስንነሳ ሻለቃ ዳዊትና ሌሎች በየጊዜው ለድህረ-ገጾች የሚጽፉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የዚህ ዐይነቱ የተሳሰተ ኢንፎርሜሽን ሰለባዎች ለመሆናቸው በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደጥንቷ አቴን የሶፊስቶች ዘመን የገዢውን መደብ ጥቅም የሚያስጠብቁና ትክክልም  ነው ብለው በማመን የሚያስተጋቡና እንድንቀበላቸውም ሙከራ የሚያደርጉ ናቸው።  ስለሆነም የሚያቀርቡትን ኢንፎርሜሽኖች በትክክለኛው መነጽር የመመርመሩ ጉዳይ ደግሞ የኛ ኃላፊነታና  የሞራል ግዴታ ይሆናል ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነቱን የውሸት ቅስቀሳና  አስተሳሰብ ዝም ብለን የምናይ ወይም የምናልፍ  ከሆነ ደግሞ ከወንጀል ነጻ አለመሆናችን ብቻ ሳይሆን፣ ህዝባችን ከድህነትና ከጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ የሚያደርገውን ውስብስብና እልክ አስጨራሽ ትግል እንዲኮላሽ አስተዋፅዖ እንደማድረግ ይቆጠራል። ከዚህ በመነሳት ትክክለኛ ነው ብዬ የማምንበትን ኢንፎርሜሽን የማቅረብ ሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታ አለብኝ።                     

     አስቸጋሪው የአፍሪካ የህብረተሰብ ታሪክ አወቃቀር !

ዛሬ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም ሆነ በኢራቅ፣ በሶሪያና በሊቢያ የሚካሄዱትን ጦርነቶች ለመረዳት የግዴታ የታሪክን ማህደር ማገላበጥ ያስፈልጋል። ወደ ኋላ ተጉዘን የነገሮችን አመጣጥ ለመረዳት እስካልቻልን ድረስ  ዛሬ በአፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱትን ጦርነቶች ለመቀበል የምንቃጣው አክራሪዎች እንደጠነሰሱት፣ የህብረተሰብ ታሪክ አወቃቀር ችግር እንዳይደለና፣ ፈረንጆች የጂ ኦ ፖለቲካ ጥቅም ትግል ነው የሚሉት ነገር እንደሌለበት አድርገን ነው የምንረዳው ወይም አምነን የምንቀበለው። የአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀርመናዊው ፈላስፋ፣ ሳይንቲስት፣ የቲዎሎጂ ምሁር፣ የህግ አዋቂና ዲፕሎማት የነበረው ጎትፍሪድ ዊልሄልም ላይብኒዝ እንደሚለው ለአንድ ነገር መከሰት አንድ ምክንያት ወይም መነሻ መኖር አለበት፤ አንድ ነገር ካለበቂ ምክንያት ሊፈጠር  በፍጹም አይችልም እንደሚለው ዛሬ በብዙ አፍሪካ አገሮች የሚካሄደው ጦርነት እንዲያው አክራሪዎች ዝም ብለው በዕብድነት መንፈስ የጀመሩት ሳይሆን የራሱ የሆነ በቂ ምክንያት አለው። ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚካሄዱት ጦርነቶች በስተጀርባ በተለይም የውጭ ኃይሎች ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወቱና፣ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ኃይሎችን በጥቅም እየገዙ ህዝብን በጎሳና በሃይማኖት አሳቦ ርስ በርሱ እንዲበላላ የማይሸርቡት ተንኮል የለም። ይህም ማለት፣ አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ለስሙ የፖለቲካ ነፃነትን ቢቀዳጁም፣ በሚሸረብባቸው ተንኮልና በሚያካሂዱትም ጦርነት የተነሳ ማከናወን የሚገባቸውን ህብረተሰብአዊ ተግባር እንዳያከናውኑ ታግደዋል።  ስለሆነም አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ቢያንስ ባለፉት 70 ዓመታት ሰላም አግኝተው ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቱር እየታገዙ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ ህብረተሰብ መገንባት ሲችሉና በዚያው መጠንም ዓለምን በቁጥጥራቸው ውስጥ ሲያደርጉ የአፍሪካ አገሮች ይህን ዐይነቱን የሰላም ዕድል ባለማግኘታቸው ያላቸውን የጥሬ ሀብትና የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ ጠንካራ ኢኮኖሚና ህብረተሰብ መገንባት አልቻሉም። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ጤናማ የሆነ ህብረተሰብ ለመመሰረት በሁሉም አቅጣጫ ውስጣዊ ሰላም መኖር አለበት። በአንድ አገር ውስጥ ያለ ህዝብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠርና ለምርት ሂደት ተጠቃሚ ለማድረግ የግዴታ በሁሉም መልክ የሚገለጽ መንፈሳዊ ነፃነት ማግኘት አለበት። ሰላም በሌለበትና መንፍሳዊ ነፃነት ባልሰፈነበት አገር ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለህብረተሰብ አወቃቀር  ወይም ግንባታ በፍጹም ማውራት አይቻልምና።

ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ከሌሎች አገሮችና አህጉሮች ጋር ሲወዳደር እንደ አፍሪካ የተሰረረ ወይም ጦርነት የታወጀበት  አህጉር በፍጹም የለም። በመጀመሪያ ደረጃ በ15ኛው ክፍለ-ዘመን በባሪያ ንግድ የተነሳ ቢያንስ ከ30-60 ሚሊዮን፣ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለከቱት ደግሞ እስከ 90 ሚሊዮን የሚደርስ ጥቁር አፍሪካዊ እየተጋዘ ወደ ምዕራብ አውሮፓና ወደ ላቲን አሜሪካ አገሮች እንደተጓዘ ይታወቃል። በዚህ አማካይነት እስከዚያን ጊዜ ድረስ ዳብሮ የነበረውና በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የስራ-ክፍፍልና የህብረተሰብ አወቃቀር ድምጥማጡ እንዲጠፋ ይደረጋል። በመተሳሰርና በመጠናከር ላይ ይገኝ የነበረው ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት በባሪያ ንግድ የተነሳ ይበጣጠሳል። በተጨማሪም በማደግ ላይ የነበረው ከላይ ወደ ታች የስልጣን ተዋረድና የስራ-ክፍፍል እንዳለ ይደመሰሳል። በጊዜው በዚህ ዐይነቱ የሰውን ልጅ እንደከበት እየነዱ መውሰድ ጠቅላላውን ጥቁር ህዝብ የሚመለከት ሳይሆን ሊሰራ የሚችለውንና በተለያየ የሙያ ዘርፍ ተሰማርቶ ህብርተሰብአዊ ሀብት ለማዳበር የሚችለውን የሰው ኃይል የሚመለከት ነበር።  በዚህም ምክንያት የተነሳ እዚያው የቀረው ሌላው ጥቁር አፍሪካዊ፣ አብዛኛዎቹ ሽማግሌዎችና ሊሰሩ የማይችሉ ስለነበሩ ሁሉ ነገር ይዘበራረቅባቸዋል። አዲስ ስርዓትም መፍጠር ይሳናቸዋል። በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የቅኝ አገዛዝ ሲስፋፋ ለዚህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ዕድገት መጨናገፍ የባሰውን ጥልቀት በመስጠት የህብረተሰብን ህግ ማዘበራረቅ ተቻለ። የአፍሪካ ገበሬዎችና አንጥረኞች እንዲሁም በንግድ ስራ ተሰማርተው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ለአውሮፓ ኢንዱስትሪ የሚሆን የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት ውጤቶቾን ብቻ እንዲያመርቱ በመገደዳቸው ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የምርት ክንውን ላይ እንዳይሰማሩ ታገዱ። በዚህም ምክንያት ወደ ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ እንዳይዳብርና እንዳይስፋፋ ታገደ። አዳም ስሚዝ እንደሚለው ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግና መዳበር የግዴታ የተለያየ ምርት በተለያዩ ሙያተኞች መመረት ያለበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ የገበያውም ስፋት እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ነው። በተጨማሪም ለምርት ማምረቻ የሚያገለግሉ ማሺነሪዎች እየተመረቱ መቅረብ አለባቸው። የማምረቻ መሳሪያዎች በብዛትና በዐይነት ሊመረቱ የሚችሉት ደግሞ በህብረተሰብ ውስጥ ነፃ ውድድር ሲኖር ብቻ ነው።  ከላይ በተዘረዘሩት ቅድመ-ሁኔታዎች አማካይነት ብቻ ነው የገበያ ኢኮኖሚ በዐይነትም ሆነ በስፋት ማደግና አንድን ህብረተሰብ ማያያዝ የሚችለው። በተጨማሪም ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ የሰውን ኃይልና የጥሬ-ሀብትን ለማንቀሳቀስ የሚችል በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ሰፋ ያለ ኢንስቲቱሽን በየቦታው መኖር አለበት። ከዚህም ባሻገር  ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት ዘመናዊ የሆነና የተቀላጠፈ የመንግስት አወቃቀርም ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት የታወቀ ጉዳይ ነው። ከዚህም ሌላ ቀስ በቀስ ዕውቀትና የማኑፋክቱር ክንዋኔ ኢንስቲቱሽናላዊ መሆንና በመንግስት መደገፍ አለባቸው። የባሪያ ንግድና የቅኝ አገዛዝ ይህንን ዐይነቱን ውስጣዊ ሂደት(Evolutionary Process)  ነው ማጨናገፍ የቻሉት። በባሪያ ንግድ የተሰማሩና ቅኝ ግዛትን ያስፋፉ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የአፍሪካን አገሮች ህብረተሰብአዊ አወቃቀር በማዘበራረቅ እስከዛሬ ድረስ ሊላቀቁ ያልቻሉትን በሽታ ነው ጥለው የሄዱት። ከዚህ ስንነሳ አውሮፓውያን በአፍሪካ ላይ ያደረጉት ወረራና ዛሬም የሚያካሂዱት ጦርነትና በተለያየ መልክ ጣልቃ መግባትና መንግስታትንና ህብረተሰብን ማዋከብ  ጤናማ የሆነን የህብረተሰብን አወቃቀርና የአገር ግንባታን ህግ የሚጻረር ነው። ዘለዓለማቸውን በድህነት ዓለም እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውና የጥሬ-ሀብታቸውም እንዲዘረፍ የሚጋብዝ ነው።

ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ እንደምዕራብ አውሮፓ አገሮች መነሻ አድርገው የሚጓዙበት መሰረት አልነበራቸውም። የየመንግስታቱ መኪናዎችም በቅኝ ግዛት አስተዳደር የተገነቡና ለአውሮፓያውያን ዘረፋ እንዲያመቹ ሆነው በመዘጋጀታቸው የተነሳ በቂ ዕውቀትና የሰው ኃይል አልነበራቸውም። በአንጻሩ ግን አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ቢያንስ የአራት መቶ ዐመት የህብረተሰብና የህብረ-ብሄር አገነባብ ልምድና ታሪክ ነበራቸው። አገሮቻቸውም ከውጭ በውጭ ኃይል በመወረር ባለመረበሹ በተለይም ከሰላሳኛው ዓመት ጦርነት በኋላ በ1648 ዓ.ም ጀምሮ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች አገሮቻቸውን በጸና መሰረት ላይ የመገንባት ዕድል ነው ያገጠማቸው። በተለይም የመርከንታሊዝምን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ለገበያ ኢኮኖሚ የሚያመች ሁለንታዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው የተከተሉት። ስለሆነም የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን የነቁ ኃይሎችን በሃሳብ፣ በዕገዳ ፖሊሲ(Protectionism) በቅናሽ ብድርና በማደግ ላይ ይገኙ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን(Infant Industries)  በደመገፍና በመንከባከብ፣ እንዲሁም  በመረባረብ ነው ብሄራዊ ኢኮኖሚ(National Economy) ለመገንባት የቻሉት። እንደሚታወቀው ኢኮኖሚ በዐይነትና በብዛት ሊያድግ የሚችለው  በደንብ የታቀዱ ከተማዎችና መንደሮች፣ እንዲሁም ካፒታልን፣ ዕቃንና የሰውን ኃይል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማመላለስ የሚያስችል የመገናኛ መንገድ ሲኖር ብቻ ስለሆነ፣ በጊዜው የመንግስታት ዋናውና ተቀዳሚው ተግባር በእነዚህ ነገሮች ላይ መረባረብ ነበር። በዚህ መልክ ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቅ ያሉት የተገለጸላቸው የፍጹም ሞናርኪዎች(Enlightened Absolute Monarchies)  ለከበርቴው መደብና ለካፒታሊዝም ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ችለዋል ማለት ይቻላል።  እንደዚህ ዐይነቱ ቅድመ-ሁኔታ ባይነጠፍ ኖሮ አዳም ስሚዝ እንደሚለን በረቀቀው እጅ ብቻ ካፒታሊዝም ማደግ ባልቻለ ነበር።

ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን አፍሪካ አንዳችም የዕረፍት ጊዜ ያለማግኘቷ ብቻ ሳይሆን፣ ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሲይዝና የተወሳሰቡ  የብዝበዛ መሳሪያዎችን ሲያዳብር የአፍሪካን ኤሊት ጭንቅላት የሚቆጣጠርበት የርዕዮተ-ዓለምና የዕውቀት ቴክኒኮችን በማዳበር በቁጥጥሩ ስር ማዋል ችሏል። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለ በኋላ በገበያ ኢኮኖሚ እየተሳበበ ህብረተሰብአዊ ሀብት ለማዳበር የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳይከተሉ በመገዳደቸው የግዴታ በአንድና በሁለት የጥሬ ሀብት ላይ ብቻ በመመካት የባሰ ጥገኛ ለመሆን በቁ። ከዚህ ዐይነቱ ጥገኝነት ለመላቀቅ ቆርጠው የተነሱ እንደነ ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ሚልተን አቦቴ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ሳንካራ ክትትል ስልተደረገባቸውና የመጨረሻ መጨረሻም እንዲገደሉ በመደረጋቸው ያሰቡትን  ህብረተሰብን በጤናማ መሰረት ላይ የመገንባቱ ህልማቸው ተጨናገፈባቸው። ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ቢያንስ ከሰባ በላይ የሚሆኑ የመንግስት ግልበጣዎችና የመንግስት ግልበጥ ሙከራዎች ተካሂደዋል። አገዛዞች እንዲከረባበቱ ተደርገዋል። ስላምና መረጋጋት እንዳይኖርና አንዱ ሌላውን እየተጠራጠረ እንዲኖር ተደርጓል። ከመጀመሪያው ትውልድ በኋላ ስልጣንን የጨበጡት አዳዲስ መሪዎች ደግሞ በምዕራቡ የስለላ ድርጅት የሰለጠኑና፣ የየመንግስታቱም መኪናዎች ቴክኖክራሲያዊ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች ስለተሰገሰጉ አንድ መንግስት መስራት ያለበትን ሀብረተሰብን የመገንባት ጉዳይ ተግባራዊ እንዳይሆን ተደረገ።  በዚያው መጠንም የአፍሪካ አገዛዞች በዓለም አገዛዝ የጭቆናና የብዝበዛ ሰንሰለት ውስጥ እንዲካተቱ በመደረጋቸው ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውን ከመገንባትና በሳይንስ፣ በቲክኖሎጂና በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ ከማዳበር ይልቅ የምዕራብ አውሮፓንና የአሜሪካንን ዕድገት አጋዥ እንዲሆኑ ለመደረግ በቅተዋል። የጥሬ-ሀብት እንዲበዘበዝ፣ ወደ ውጭ ከሚሸጠው የጥሬ-ሀብት ከሚገኘው ገንዝብ ውስጥ የተወሰነውን የውጭ አገር ባንክ እንዲቀመጥና የካፒታሊስት አገሮችን ባንክ እንዲደልቡ ለማድረግ ሲቻል፣ በዚያውም መጠንም ከውስጥ ወደ ውጭ  የሀብት ሽሽት(Capital flight) እንዲካሄድ በመደረጉ የአፍሪካ አገሮች መፈናፈኛ እንዳያገኙ ለማድረግ ተችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን ባልተስተካከለ ንግድና(Unequal Exchange) በዕዳ በመጠመድና የወለድ ወለድ በመክፈል አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በተለያየ መሳሪዎች እንዲራቆቱ ተደረጉ። በተለያዩ ጊዜያት በገበያ የኢኮኖሚ ስም የሚወጡ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የአፍሪካ አገሮችን ሁኔታ የባሰውኑ የሚያዘበራርቁ፣ ሀብት እንዲባክን የሚያደርጉና፣ በዚያው መጠንም የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማደለብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቱ በህዝቡ ላይ አጠቃላይ የሆነ ጦርነትና የባህል ውድመት እንዲያደርግ ተገደደ።

ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ተጓትቶ እዚህ የደረሰ አገሮችን ወደ ኋላ የሚጎትት፣ ወይም ደግሞ እዚያው በዚያው እየተንደፋደፉ የሚያስቀራቸው መንግስታዊ አወቃቀርና የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የተዘበራረቁ፣ ግን ደግሞ ለብሄራዊ ሀብት መዳበርና ለብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት የማያመቹ ተሰበጣጥረው የሚካሄዱ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች እንደ አሸን እንዲፈልቁ ተደረጉ። እነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንፎርማል ሴክተርና ከእጅ ወደ አፍ የኢኮኖሚ ክንዋኔ በመባል የሚታወቁ ሲሆን በመሰረቱ የካፒታሊዝምን ህግ ተከትለው የሚያድጉ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች አይደሉም። በመሆኑም ለቴክኖሎጂዎች ዕድገት፣ ለመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ፣ ለነፃ ውድድር፣ ለስራ መስክ መከፈት በፍጹም የሚያመቹ አይደሉም። በአንድ አገር ውስጥ በተለያዩ  ከተማዎች ውስጥ ከመስፋፋታቸውም የተነሳ ራሳቸውም ድህነትን ቀራፊ ከመሆን ይልቅ የድህነት ምንጭ ሊሆኑ በቁ። በዚህም የተነሳ ባህላዊ ዕድገትና የፈጠራ ስራ ሊዳብሩ በፍጹም አልቻሉም። በዚህ ዐይነቱ ውጥንቅጡ በወጣ ሁኔታ ውስጥ በኒዎ-ሊበራሊዝም ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች የባሰውኑ ነው የሚያዘበራርቀው። በተለይም ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር ተጎትተው የሚመጡ እንደ ግሎባላይዤሽንና የነፃ ንግድ የመሳሰሉት የየአገሮችን የማምረት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሱና፣  ከተማዎችም እንዲዝረከረኩ የሚያደርጉ ናቸው። ይህ በራሱ ደግሞ የሴተኛ አዳሪዎችንና፣ በተለያየ መልክ የሚገልጹ የብልግና ተግባርና ሸፍጠኝነት እንዲስፋፋ ነው የሚያደርገው። ይህም ማለት በተለይም ባለፉት 40 ዓመታት ካፒታሊዝም በተለያዩ አገሮች ሲስፋፋ መልዕክቱ ወይንም ዋናው ተግባሩ በየአገሮች ውስጥ የተስተካከለ ዕድገትንና፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ስልጣኔና የባህል ተሃድሶ ማምጣት ሳይሆን የባህል ውድቀትንና የአገሮችን መዘበራረቅንና መፈረካከስን ነው ያስከተለው።

ይህ በራሱ ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዘራፊና አምባገነናዊ  የሆኑ፣ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ፈሺሽታዊ የሆኑ አገዛዞች- የዛሬውን የወያኔን  ፋሺሽታዊ  አገዛዝ ና ዘራፊነት መገንዘቡ አስፈላጊ ነው-  ብቅ እንዲሉና እንዲጠናከሩ አስቻላቸው። የመንግስትን ሚና ያልተረዱ አንድ ወጥ መንግስታት፣(one party rule) ወይም ደግሞ በምርጫ ስልጣንን የሚይዙና፣ ህገ-መንግስቶቻቸው እንደገና በመጻፍ የስልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝሙ የመንግስትን መኪናና ፖለቲካን ወደ ግል-ሀብትነት በመለወጥ የየአገሮቻቸውን ሀብት እንዲዘርፉና ወደ ውጭ እንዲያወጡ ሲያስቻለቸው፣(Predatory States)፣ በዚያው መጠንም ህዝቦቻቸውን በማድኸየትና የህሊናና የአካባቢ ውድመት በማድረስ ህዝቦቻቸውን አቅመ-ቢስ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን ተከታታዩ ትውልድ መሰረት አድርጎ ሊጓዝበት የሚችል መሰረት ጥለው ማለፍ እንዳይችሉ ተደረጉ። በዚህ ዐይነቱ የሀብት ዘረፋና አገሮችን ማዘበራረቅ፣ እንደ ተራድዖ ድርጅት(NGOs) የመሳሰሉት፣ በጥሬ-ሀብት ማውጣት የሰለጠኑ ትላልቅ የምዕራብ አውሮፓና የአሜሪካ እንዲሁም የካናዳና የአውስታራሊያ ኩባንያዎች፣ ምክር ሰጭ ነን ባይ ድርጅቶችና፣(Consulting Companies) በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ስልት የሰለጠኑና በሙስና ውስጥ የዘፈቁ የየአገሩ ኤሊቶች በመመሰጣጠር የአፍሪካን ሀብት እየዘረፉና ህዝብን እያደኸዩ ነው። እንደ ሲአይ ኤ፣(C.I.A) ሞሳድና የእንግሊዙ  የስለላ ድርጅት በየአካባቢው የዚህ ወይም የዚያ ጎሳ አባል ነኝ የሚለውን ምስኪን ህዝብ እያሰለጠኑና ርስ በርሱ እንዲዋጋ በማድረግና፣ በዚያው መጠንም ስትራቴጂ የሆኑ የጥሬ-ሀብቶችን ቆፍረው በማውጣትና ወደ ውጭ በመላክ አፍሪካ በፍጹም እንዳንተሰራራ ለማድረግ በቁ። ይህንን የአፍሪካ ዘረፋ በሚመለከት ከአንድ ዓመት በፊት በእግሊዛዊው ቶም በርጊስ(Tom Burgis) የተጻፈውን የአፍሪካን ሀብት ዘረፋ(The Looting Machine)  የሚባለውን መጽሀፍ መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው።

በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ይህ ዐይነቱን በየአገሩ መንግስታትና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና፣ የምዕራብ መንግስታትና እንዲሁም በተለያዩ ድርጅቶች የሚደረገውን ዘረፋ፣ ህብረተሰብአዊና ባህላዊ እንዲሁም የአካባቢ ውድመት ለመጋፈጥ የሚችል ኃይል በአገር አቀፍ ደረጃ አለመኖሩ ነው። የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች በተናጠል በመሆናቸውና ሰፋ ያለ የሳይንስ፣ የፍልስፍናና የቴዎሪ መሰረት ስለሌላቸው ትግሉን ማስተባበርና አገር አቀፋዊ የሆነ ጠንካራ የሲቪል ማህበርሰብ እንቅስቃሴ ሊፈጠር አልቻለም። የሚፈጠሩትም ተናጠል ድርጅቶች ቶሎ ብለው ከውጭ መጥተው እንረዳለን ብለው በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ስለሚታለሉና የነሱንም ምክር ስለሚሰሙ በየአገሩ ያለውን እንቅስቃሴ ሰፊ የሆነ የሳይንስና የቲዎሪ መሰረት መስጠት አልተቻለም። በተለይም በኢኮኖሚ ቲዎሪና  ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ የሆነ  ክፍተት በመኖሩ በገበያ ኢኮኖሚ ስም ተሳቦ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ተረቆ የሚመጣውን ፖሊሲ በሚገባ ለመጋፈጠና ለማጋለጥ በፍጹም የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። በእነዚህ ድርጅቶች በተደጋጋሚ እየረቀቀ የሚመጣው ፖሊሲ አንድም ጊዚና አንድም አገር ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በማኑፋክቱር ላይ የተደገፈ ሰፋ ያለና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት አለመቻሉን እየታወቀ ራሳቸው በአንድ ወቅት የማርክሲዝምን አርማ ይዘው ሲታገሉ የነበሩ ሁሉ ነገረ-ዓለሙን በመተውና በኬይንሲያንና በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች እየታለሉ የጥፋቱ ተባባሪ ለመሆን በቅተዋል። ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም የመርከንታሊስት፣ የፊዚዮክራትስ፣ የክላሲካል፣ የማርክሲት፣ እንዲሁም ኢቮሉሸናሪ የኢኮኖሚክስ ዕድገትና የፊዚካል ኢኮኖሚክስ ትምህርት በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት መልክ መሰጠታቸው እየታወቀ በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ላይ የተመሰረተ ትምህርት ስለተስፋፋና የብዙዎችን ጭንቅላት አንቆ በመያዙ የተማረውና ፖሊሲ አውጭዎች በሙሉ ካለዚህ በስተቀር ምንም አማራጭ የሌለ እየመሰላቸው የአንድን ትውልድ ብቻ ሳይሆን፣ የሶስትና የአራት ትውልድን ታሪክና ዕድል እያበላሹ ነው። በአጭሩ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሰፋ ባለ የዕውቀት መሰረት ላይ፣ ማለትም በፍልስፍናና በተፈጥሮ ሳይንስ ላይ ተመርኩዞ ጥናትና ክርክር ስለማይደረግ በየአገሮች ውስጥ ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይል ሊዳብር አልቻለም። በዚህም የተነሳ በየአገሮች ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች አለኝታ የሚሆናቸውና የሚያስተምራቸው ሰው በማጣታቸው ከውጭ በሚመጡ ዜጎች እንደ ሰው የማይቆጠሩበት ደረጃ ደርሰዋል። ሀብቶቻቸው እየተዘረፈና ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ መበላሸት እየደረሰ ነው። ህዝቦች በየአካባቢው መኖሪያ እንዲያጡ፣ ንጹህ አየር እንዳይተነፍሱና ንጹህ ውሃ እንዳይጠጡ እየተደረገ ነው።

ከዚህ ስንነሳ ካለፉት አስርና አስራ ዓምስት ዐመታት ጀምሮ በተለያየ መልክ የሚካሄደውን፣ በመሰረቱ ከህብረተሰብ መናጋትና፣ ጠንካራ ኢኮኖሚና ኢንስቲቱሽን አለመኖር ጋር የተያያዘውን ጦርነት ስንመለከት ዋናው መነሾው በአማካይ ጎኑ በኢምፔሪያሊስቶች የተሸረበ ወይም የተጠነሰሰ ሴራ ነው ማለት ይቻላል። ነገሩ ቀላል ነው። ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ በተለይም ስትራቴጂ የሆኑ እንደ ኮልታን፣ ዲያመንድና ወርቅ፣ መዳብ፣ ቦክሳይትንና እነዚህን የመሳሰሉትን የጥሬ-ሀብቶች ማግኘት የሚችሉት አፍሪካ በጦርነት ስትታመስ ብቻ ነው። በተጨማሪም እንደቡና፣ ካካኦ፣ ኦቾሎኒ፣ ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ስኳር፣ ማንጎና ፓፓዬ፣ እንዲሁም አበባ ማግኘት የሚችሉት ያለው ሁኔታ ሲጣነከርና አፍሪካም በውዝግብ ዓለም ውስጥ ስትገኝ ብቻ ነው። በአንፃሩ የአፍሪካ ኢኮኖሚ የሚያድግና መሰረቱም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከሆነ ይህ ዐይነት ዕድገት የጥሬ-ሀብትን ወደ ውጭ መውጣት ስለሚቀንስ የአፍሪካ ዕድገት ቀጭጮ መቅረት አለበት።  የአፍሪካ ህዝቦች የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት ውጤቶችን ብቻ በማቅረብ እንደባሪያ እየታዩ መኖር አለባቸው። እግዚአብሄር የሰጣቸውን ነፃ አስተሳሰብ በመጠቀም ነፃና ጤናማ፣ እንዲሁም ተከታታዩ ትውልድ የሚኮራበትን ህብረተሰብ መገንባት የለባቸውም።  ይህ አጠቃላዩ ሁኔታ ነው ዛሬ በአፍሪካ ምድር ውስጥ ለተስፋፋው ጦርነት ምክንያት የሆነው። ከዚህ ውጭ ማሰብና የአፍሪካን አገዛዞች እንደጭራቅ ማየትና የሚሆን የማይሆን ነገር እየጻፉ ታዳጊውን ትውልድ ማወናበድና ህዝብን ማደናገር ወደድንም ጠላንም የሰላዮችንና የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ጨዋታ እንድንጫወት የሚያደርገን። ሳንወድ በግድ በነሱ የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመጠመድና እነሱ የሚሉትን በማስተጋባት ታሪክ እንዳይሰራ ነው መንገዱን ሁሉ የምንዘጋው። በተለይም በኢትዮጵያ ምሁሮች ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር  የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ አወቃቀር ውስብስብነትና የስልጣኔና የዕውነተኛ ነፃነትን  ጠንቅነት ለመረዳት ጥረት አለማድረግ ነው። ሰለጠነ የሚባለው የምዕራቡ አውሮፓውና የአሜሪካኑ የነጭ ኦሊጋርኪ መደብ የሚለውና የሚሰራው ሁሉ ትክክል ነው። ወንጀል ቢሰራም ይህ እንደ ወንጀል መቆጠር የለበትም፤ ምክንያቱም ይህ ዓለምን የሚያተራምሰው ኃይል ከእግዚአብሄር  ፈቃድ ስለአገኘ እሱ የሚለውንና የሚያደረግውን ዝም ብለን እንመልከት መንፈስ የተስፋፋ ይመስላል። ስለሆነም ይህንን እያነሱ መታገል፣ ወይም ትችታዊ በሆነ መልክ መጻፍ የአምላክን ህግ እንደመጣስ ይቆጠራል፤ ተግባሩም የአናርኪስቶችና የአክራሪዎች ነው ይሉናል። የኛ ተግባር ቦንብ ሲጣልብን፣ ህዝቦቻችን ሲገደሉብን፣ አምባገነን አገዛዞች ከላያችን ላይ ተቀምጠው ታሪክን ሲያከረባብቱና ባህልን ሲያበላሹ ዝም ብሎ መመለክት ነው። ሀብት ሲወድም፣ ሲዘረፍና አካባቢ ሲቆሽሽ ይህ ለጥቁር ህዝብ የተሰጠ ጸጋ ስለሆነ ዝም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ነው ይሉናል።   በዚህ ቅስቀሳና ስም ማጥፋት፣ ወይንም ሰውን ማንቋሸሽ ከሁሉም አቅጣጫ የተወሳሰቡ ነገሮችን እያነሳን እንዳንመረምርና ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ እንዳንከራከርባቸው ታግደናል። አማራጭ መንገድም ማሳየት እንዳንችል ተደርገናል። ወይም ስናሳይ ደግሞ የዕብዶች ስራ ነው ይሉናል። እንደዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ቦታ የለውም፣ ከላይ የመጣን ትዕዛዝ የሚፃረር ስለሆነ ተቀባይነት የለውም ይሉናል። በዚህ መልክ በረቀቀና በግልጽ በሚካሄድ ትግልና የስም ማጥፋት ዘመቻ ኃይል እንዲበታተን ተደርጓል። ሀቀኛውን የሳይንስና የነፃነት ፈለግ እንዳንከተል ታግደናል።  ከዚህ ስንነሳ ለፖለቲካ ስልጣን እታገላለሁ የሚለውና እምዬ ኢትዮጵያ እያለ ባንዲራን የሚያውለበልበው በመሰረቱ የኢትዮጵያን ህዝቦች ዕድል የሚመለከተው በአሜሪካን መነጽር ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድና የነገሮችን ሂደት በጥቁርና በነጭ እየቀቡ ማየት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ግንዛቤን የሚጻረር ነው። ለአገር ግንባታ ዕንቅፋት የሚሆንና፣ አንድ ህብረተሰብ ለዝንተ-ዓለሙ ተዝረክርኮ እንዲቀር የሚያደርግ ነው።  የሰው ልጁ ሁሉ በእግዚአብሄር አምሳል ነው የተፈጠረው፣ ስለሆነም ሁሉም ሊያስብ፣ ሊፈጥር፣ የራሱን አገር ተፈጥሮአዊ ሀብት አውጥቶ በሃይልና(Energy) በማሺን አማካይነት በመለወጥ ለራሱ መጠቀሚያ ሊያደርግ ይችላል፣ እያንዳንዱ አገር የየራሱን ጠቃሚ ባህልና ታሪክ መንከባከብ አለበት፣ በመሆኑም ራሱ በመሰለው መንገድ ህብረተሰቡን ማደራጀትና ታሪካዊ ስራዎች ሊሰራ ይችላል የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ የሚፃረር ነው።  የሻለቃ ዳዊት ችግር ይህንን መሰረታዊ የእግዚአብሄር ቃልና ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብን የሚፃረር ነው። እየተቃጠልን፣ እየበገንና እየተሰደድን እንድንኖር የሚያደርገን ነው። ባጭሩ አቀራረቡ ፀረ-ስልጣኔ፣ ፀረ-ሳይንስ፣ ፀረ-ፍልስፍና፣ ፀረ-ባህልና ፀረ የሰው ልጅ ነው። ልንከተለው የሚገባን አይደለም።

አክራሪ የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋትና ጦርነት !

አባዛኛዎቻችን የታሪክን ሂደት ላልተከታተልንና ለማንከታተል የእስልምናን ሃይማኖት የውዝግብና የጦርነት ምንጭ አድርገን ነው የምንቆጥረው።  ሃቁ ግን በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአገራችን ምድር ውስጥ የክርስትና ሃይማኖት ሲገባ ከዚህ በፊት ሌላ ዕምነት የነበረውንና አልቀበልም ያለው እየተገደደ ነው የክርስትናን ሃይማኖት እንዲቀበል የተደረገው። በአገራችን ምድር በዘጠነኛው ዓመተ-ምህርት ለዮዲት መነሳትና ለአክሱም ስልጣኔ መውደም አንደኛው ምክንያት በአራተኛው ክፍለ-ዘመን የክርስትና ሃይማኖት ወደ አገራችን ሲገባ  ህዝቡ እንዲቀበለው ጉልበት ስለተጨመረበትና የተወሰነውም ከፍተኛ ጥቃት ስለደረሰበት ነው። የዮዲትም አነሳስ ይህንን በአራተኛው ክፍለ-ዘመን በሷ ጎሳ ላይና ሌላ ዕምነት ይከተል የነበረውን ሃይማኖቱን እንዲለውጥ በመገደዱ ለመበቀል ነው።  በአውሮፓ ምድርም የክርስትና ሃይማኖት ሲገባ ነገስታቱ አልቀበልም ያለውን ሁሉ ቋንጃውን እየሰበሩ ወይም ደግሞ አንዳንዱን በመግደልና የተቀረውን በማስፋራራት ነው የክርስትናን ሃይማኖት ማስፋፋት የቻሉት። በተለይም የካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነትን በተጎናፀፈበት በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን በምዕራብ አውሮፓ ሴቶች እንደ ልዩ ፍጡር እየታዩና ለብዙ ነገሮች ጠንቅ ናቸው እየተባሉ ይቃጠሉ እንደነበር ግልጽ ነው። ይህ ዐይነቱ አጸያፊ ድርጊት በእስልምና  ሃይማኖትና በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተለመደ አልነበረም።  በአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በተለይም አንዳሉሲያ በሚባለው በደቡቡ የስፔን ክፍል በተገለጸላቸው የእስላም መሪዎችና አዋቂዎች የዳበረው ስልጣኔ ድምጥማጡ ሊጠፋ የቻለው የክርስትናን ሃይማኖት በሚከተሉ አማኞችና መሪዎቻቸው አማካይነት ነው። የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በእስላሙ ህዝብና በስልጣኔው ላይ በመዝመታቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ህይወቱ እንዲጠፋና ስልጣኔውም እንዲወድም ተደርጓል። የኋላ ኋላም ለስፔን ወደ ኋላ መቅረት አንደኛው ምክንያት በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን አይሁዲዎችና የእስላም ምሁሮች በፊዩዳሎችና በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች በመባረራቸው ነው።  የስፔን ቅኝ ገዚዎች ወደ ደቡብና ወደ ማዕከለኛው አሜሪካ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ሲሄዱ፣ በአንድ በኩል የካቶሊክን ሃይማኖት ለማስፋፋት ሲሆን፣ በዚያውም መሰረት የእነዚህን አገሮች የወርቅና የብር ክምችት ለመዝረፍ ነው። በዚህ መልክ የኢንካና የማያ ስልጣኔዎች እንዲወድሙ ተደርገዋል። የስፔን ወራሪዎች ከአገራቸው ይዘው በመጡት የአባለ-ዘር በሽታ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የየአገሩ ሰዎች አልቀዋል።  በአጭሩ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ድረስ በዓለም አቀፍ ደራጃ የተካሄዱት ጦርነቶች የክርስትናን ሃይማኖት እከተላለሁ፣ ስልጣኔም አለኝ ብሎ በሚዘባነነው በምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች አማካይነት ነው። የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶትችም የተቀሰቀሱት የመሸበት ስልጣኔ ተስፋፍቷል በተባለበት በምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም በጀርመን ነው። የቅኝ ግዛት አስተደዳሪዎች ወደ አፍሪካ ስተት ብለው ሲገቡ በአንድ እጃቸው ሰይፍ፣ በሌላው እጃቸው ደግሞ የመጽሀፍ ቅዱስን በማንገብ ነበር። ከዚህ ስንነሳ የእስልምና ሃይማኖት እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመንና እስከዛሬም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለተስፋፋው ቀውስና ስለተደረገው የሰው ልጅ ዕልቂት ተጠያቂ ልናደረገው በፍጹም አንችልም። በሌላ ወገን ግን በመጽሀፍ ቅዱስም ሆነ በቁራን ውስጥ ሃይማኖትን ለማስፋፋት የግዴታ ጉልበትን ተጠቀም፣ ጦርነትን አውጅ፣ ሰውን ስትገድል ብቻ ነው ሃይማኖትን ማስፋፋት የምትችለው የሚል ቃል ተጽፎ አይገኝም። በተሳሳተ መልክ ሃይማኖት ወደ ርዕዮተ-ዓለምነትና የአገዛዝ መሳሪያነት በመቀየሩ፣ የሞራል መስበኪያና የሰላምና የብልጽግና ማስፋፊያ መሳሪያ መሆኑ ቀርቶ የአመጸኞችና ስልጣንን የጨበጡ መሳሪያ ሊሆን በቅቷል።

ሻለቃ ዳዊት ወዳነሳው ነጥብ እንምጣና በመጀመሪያ የናይጄሪያን ጉዳይ እንመልከት። በናይጄሪያ የአክራሪነት መሰረቱ የተጣለው እንግሊዞች የቅኝ ገዢዎች በነበሩበት ዘመን ነው። በጊዜው በሰሜኑና በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ የእስልምና ሃይማኖት የተስፋፋ ስለነበር እዚያ በነበረው የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አስተዳደር የምዕራቡ ዕውቀት ሆን ተብሎ እንዳይገባና እንዳይስፋፋ ተደረገ ወይም ታገደ። በዚያን ዘመን በሰሜኑ የናጄሪያ ግዛት የቁራን ትምህርት ብቻ ነበር እንዲስፋፋ የተደረገው። የአንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ዋናው ዓላማ ብዝበዛና የአልተስተካከለ ዕድገትን ማስፋፋት ስለነበር፣ ብዝበዛውን ለማጠናከርና እያደገ የመጣውን የእንግሊዝ እንዱስትሪ በጥሬ-ሀብት ለመመገብ አማራጩ መንገድ ይህንን የመሰለውን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ መከተልና ህዝብን ርስ በርሱ እንዳይተማመን ማድረግ ነበር።  ከረጅም ጊዜ አንፃር ደግሞ ይህ ሁኔታ እየተወሳሰበ በመሄድ እነሱ አንድ ቀን ለቅቀው ሲወጡ ህብረተሰብአዊ ትርምሱ ጥልቀት በማግኘት ለማስተዳደር  እንዳያመች ታስቦ ነው።  ስለሆነም በጊዜው የእስልምናን ሃይማኖት የሚያስፋፉ መሪዎች ከምዕራቡ የሚመጣውን ዕውቀት በማውገዝና የብልግና ማስፋፊያ መሳሪያ አድርገው በመስበካቸው ይህ ሁኔታ የግዴታ ቀስ በቀስ  አክራሪነትን የሚያጠናክር ሊሆን በቃ። ናይጄሪያ ነፃ ስትወጣ የዘይት ሀብት በመገኘቱና፣ በተለይም ከ1970ዎች መጀመሪያ ጀምሮ በዶላር ስትጥለቀለቅ ከዘይት ሽያች የተገኘውን ገንዘብ በእኩል ደረጃ በሰሜንም ሆነ በተቀረው የናይጄሪያ ክፍል ስርዓት ያለው ዕድገት እንዲስፋፋ በማድረግ የሶሻል ቀውስ እንዳይፈጠር አስፈላጊው እርምጃዎች ባለመካሄዳቸው፣ በተለይም ተበድያለው ለሚለው የሰሜኑ ክፍል ቅሬታን አስከተለ። የዘይት ሀብት መገኘትና ሙስና መስፋፋት የማህበራዊ ቀውስ እንዲስፋፋና በህዝቡ ዘንድ መጠላላት እንዲጠናከር ለማድረግ በቃ። ለጦርነትም መነሾው ተራው የእስልምና ሃይምኖት ተከታይ ህዝብ ሳይሆን መሪ ነን የሚሉና ከክርስቲያኑ የሃማኖት መሪዎች ጋር የሚፎካከሩ ናቸው። በአንፃሩ መሪዎቹ የተደላደለ ኑሮ ሲኖሩ የተቀረውን ህዝብ ያተራምሳሉ። ጦርነቱ እንዲፋፋም ያደርጋሉ። ይህ ዐይነቱ ያልተሰተካከለ ዕድገት ተበድያለው ለሚለው የናጄሪያ የሰሜኑ ክፍል ሁኔታውን እንዲጠቀም በማድረግ ጦርነት እንዲከፍት አደረገው። በጦርነት ውስጥ ተሰማርተው የዕውር ድንብራቸውን ዝም ብለው ህዝብን የሚያርዱት የቦኮ ሃራም ተዋጊዎች  የመጨረሻ ዓላማቸው ምን እንደሆን በፍጹም አይታወቅም። ይሁንና ግን በናይጄሪያ ውስጥ በእስልምና ሃይማኖት ስም ተሳቦ የሚካሄደው ጦርነት የባሰውን እንዲካረር የውጭ ኃይሎችም እጅ እንዳለበት በቂ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። በተለይም የናይጄሪያን በህዝብ ቁጥር ማደግ የሚፈራው አሜሪካ በ1975 ዓ.ም በእነ ሄኔሪ ኪሲንጀር በተጠናቀረው ጥናት መሰረት እንደናይጀሪያ የመሳሰሉትን አገሮች በጎሳና በሃይማኖት ስም አሳቦ ዘለዓለማዊ ጦርነት ውስጥ  እንዲዘፍቁ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው። በዚህም አማካይነት የህዝብን ቁጥር ማደግ መቆጣጠር ወይም መቀነስ ይቻላል የሚል ዕምነት በአሜሪካ የፖለቲካ ኤሊት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።  ስለሆነም የአሜሪካን የስለላ ድርጅት ከእነ ቦኮ ሃራም በስተጀርባ እንዳለበት ግልጽ ነው።  በተጨማሪም የሳውዲ አረብያ መንግስት አክራሪ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን እያሰለጠነች በማስገባት ጦርነቱ እንዲስፋፋና እንዲፋፋም፣  የናይጄሪያም መንግስት ሊቆጣጠረው እንዳይችል ማድረጓ የታወቀ ጉዳይ ነው። ይህንን ሁኔታ ለመቋቋም ግራ የተጋቡት በየጊዜው ስልጣንን የሚይዙት የናይጀሪያ መሪዎች ሁኔታውን ለማብረድ ስታራቴጂ ማውጣት ስለማይችሉና አንዴ የተዘረጋው የሙስና ስርዓትም ስለማይፈቅድላቸው ሁኔታው ሪጂናዊ ባህርይ እንዲኖረው ወደ ካሜሩን ድረስ እንዲዘልቅ ለማደረግ በቅተዋል። ይህንንም ሁኔታ የፈረንሳይ የስለላ ድርጅት በመጠቀም ካሜሩን ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍን እርኩስ ስራ እንደሚሰራ የፈረንሳይ ቲንክታክ ድርጅቶች ነገሩን እያፍረጠረጡ በየጊዜው ያወጣሉ።

ከዚህ ስነንሳ በናይጄሪያና በአካባቢው በሃይማኖት ስም ተሳቦ የሚካሄደው ሰውን በጭፍን የመግደሉ ተግባር የብዙ ኃይሎች እጅ እንዳለበት ነው። ለዚህ ደግሞ በቂ ማስረጃዎች አሉ። የናይጄሪያ መንግስትም የቦኮ ሃራም አክራሪዎች የከፈቱትን ጦርነት ለመቋቋምና የመጨረሻ መጨረሻ በአሸናፊነት ለመውጣት የያዘው ስልት ለመከላከያና ለፀጥታ የሚወጣውን ወጪ የባሰውን ከፍ ማድረግና የጭቆና መሳሪያውን ማጠናከር ሲሆን፣ በዚያው መጠንም ለሶሻልና ለትምህርት፣ እንዲሁም ለዕድገት የሚመደበውን በጀት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ነው።  የመንግስቱ መኪና ባልተገለጻለቸው ሰዎች በመያዙና ሙስናም በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋ በመሆኑ፣ በአንድ በኩል የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ተንደላቆ ይኖራል፤ በሌላ ወገን ደግሞ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ውጭ ይሸሻል። ከሚሸጠው የዘይት ሀብት ደግሞ ወደ 19 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ውጭ አገር ይቀራል፣ ወይም ይጠፋል። ይህም ማለት የናይጀሪያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለመገንባትና ህብረተሰብአዊ ቀውሱን ለማብረድ የሚጠቀምበት የኢኮኖሚ መሳሪያ በጣም የተወሰነ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር ዘይት ለማውጣት የተሰማሩ የአሜሪካንና እንዲሁም የእንግሊዝና የኔዘር ላንድና የፈረንሳይ ኩባንያዎች ዘይቱን አውጥተው ወደ ውጭ ከመውሰድና እዚያው አጣርተው የራሳቸውን ሀብት ከማካበት በስተቀር ለናይጄሪያ ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አስተዋፅዖ በፍጹም ቁጥር ውስጥ የሚገባ አይደለም። በተቃራኒው ግን በከፍተኛ ደረጃ የአካባቢ ውድመትንና ከፍተኛ የሆነ ህብረተሰብአዊ ቀውስን እየፈተሩና ኤሊቱንም እያባለጉ ነው። በናይጄሪያ ውስጥም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዋናው ዓላማ በተሰማሩበት አገሮች ውስጥ የተስተካከለ ዕድገትን ማምጣትና ብሄራዊ ሀብት መፍጠር ሳይሆን፣ የጥሬ-ሀብትን በመዝረፍ ድህነትን ማስፋፋትና ህብረተሰብአዊ እሴትን ማውደም ነው። በዚያው መጠንም የየአገሬው ህዝብ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ማድረግ ነው። ወደ ማሊም ስንመጣ ተመሳሳይ ሁኔታን እንመከታለን።

በመጀመሪያ ማሊ በቆዳ ስፋት በጣም ትልቅ አገር ስትሆን፣ አስራሁለት ሚሊዮን ህዝብ ብቻ የሚኖርባት አገር ናት። የቆዳ ስፋቷም አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ አርባ ሺህ አንድ መቶ ዘጠና ሁለት ካሬ ሜትር(1 240 192 km2 ) ነው። ከፍተኛ የሆነ የወርቅና የዩራኒየም እንዲሁም የጋዝ ክምችት እንዳላት የታወቀ ጉዳይ ነው። ማሌ ነፃነቷን የተቀዳጀትው በፈረንጆች አቆጣጠር በሀምሌ ወር 1960 ዐ.ም ሲሆን፣ የመጀመሪያው ፕሬዜደንት ሞዲቦ ኪዬታ ናቸው። ሞዲቦ ኪዬታም የማሊን ኢኮኖሚ መሰረት ሰፋ ለማድረግ ሲሉ ሶሻሊስታዊ የሆነ የዕቅድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋሉ። በመቀጠልም ከፈረንሳይ ቁጥጥር ስር ሙሉ በሙሉ ለመላቀቅ በፈረንሳይ ስር ከተጠቃለለው ከፍራንክ የከረንሲ ወይም ገነዘብ አንድነት ለቅቀው በመውጣት የራሳቸውን ገንዘብ በማተም ነፃ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ ይጀምራሉ። ይሁንና ግን  በቅኝ ግዛት ዘመን ከተገነባው የመንግስት አስተዳደር ሙሉ በሙሉ  ለመላቀቅ ባለመቻላቸው ያለሙትን የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ተግባራዊ ሊያደርጉ በፍጹም አልቻሉም። ስለሆነም ከ7 ዓመት ሙከራ በኋላ ወደ ፈረንሳዩ የከረንሲ አንድነት በመመለስ ጥገኛ እንዲሆኑ ይገደዳሉ። ሞዲቦ ኪዬታ በወጣት መኮንኖች በ1968 ዓ.ም ይገለበጣሉ። እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ ማሊ በኮለኔል ሞሷ ትራኦሬ በሚመራ የመኮንኖች ስብስብ ትደዳደራለች።  በ1980 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ይህ አገዛዝ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) በመገደድ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋል። ይሁንና ግን ይህ የሞኔተሪ ፖሊሲ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል ይልቅ እንዲባባስ  ያደርገዋል። ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የማሊ ህዝብ ሰፋ ያለ የዲሞክራሲ የጥገና ለውጥ  ዕድል ያገኛል። በ1992 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ የሲቪል አስተዳደር ቦታውን ይወስዳል። ከዚያ በኋላ በማሊ ውስጥ በተከታታይ ከአራት በላይ የሚሆኑ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በ2012 ዓ.ም በተለይም በሰሜን ማሊ ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ አማዱ ቱማኒ ቱሬ የሚባለው ፕሬዚደንት አሜሪካን ሰልጠኖ በመጣ አማዱ ሳንጎ በሚባል መኮንን ይገለበጣል። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ በተለይም በሰሜን ማሊ ያለው ቀውስ ይባባሳል። በተለይም የማሊ መንግስትና የማሊ ኢኮኖሚ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በፈረንሳይ መንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ በመሆናቸው ነፃ ናቸው የሚያስብላቸው ሁኔታ አልነበረም።  እንደተቀሩት አስራሶስት የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አገሮችም  ማሊም በራሷ ኃይልና ተነሳሽነት ነፃ የሆነ የኢኮኖሚና የሞኔተሪ ፖሊሲ መከተል የምትችል አገር አይደለችም። የአገሯ ገንዘብ ቀድሞ ከፍራንክ ጋር አሁን ደግሞ ከኦይሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ይህ ዐይነቱ የገንዘብ መተሳሰር በተለይም ወደ ውጭ በምትልከው የምርት ውጤት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያደርጋል። በሌላ አነጋገር፣ ኦይሮ ጠንካራ ገንዘብና ከሌሎች ከረንሲዎች ጋር ሲወዳደር ውድ በመሆኑ የማሊም ከረንሲ ከዚህ ጋር የተጣበቀ በመሆኑ ማሊ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት ስለሚወደድ እንደፈለገችው ብዙ ምርት መሸጥ አትችልም። ከዚህም ባሻገር ከወጭ ንግድ የሚገኘው የውጭ ከረንሲዋና ወርቅ ከ60 % በላይ የሚሆነው በቀጥታ ወደ ፈረንሳይ ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ የሚገባ ወይም የሚተላለፍ ነው። ስለሆነም በተለያየ ጊዜ ስልጣንን የጨበጡ የማሊ ገዢዎች ነፃ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊስ በመከተል ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚና ለህብረተሰቡ የስራ ዕድል የሚሰጥ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መከተል አልቻሉም። ህዝቡን በተለያየ የኢኮኖሚ መስክ በማሰማራትና በመያዝ የማህበራዊ ቀውስና በሃይማኖትም ተሳቦ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዳይከሰት መሰረታዊ እርምጃዎች ሊወስዱ በፍጹም አልቻሉም።

ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በማሌ የሚካሄደው ጦርነት መሰረቱ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ዘመን የተጣለ ነው። በተለይም የሰሜኑ የማሊ ክፍል ታውሬግ በሚባሉ ጎሳዎች ቁጥጥር ስር ያለና ወደ ውስጥ ደግሞ የሚካሄደውን ንግድ ታውሬጎች የሚቆጣጠሩት ነበር። ፈረንሳይ በቅኝ ገዥነት ቀስ በቀስ ማሊን ስትቆጣጠር ይህንን የታውሬግን የበላይነት በመገልበጥ በተለይም ከዚህ በፊት በቁጥሩ አናሳ በሆነ ጎሳ እንዲገዙ ይገደዳሉ። ይህ ሁኔታ የውስጥ ንግድንና በተለይም የሰሜኑን የማሊን ክፍል ለሚቆጣጠሩት የታውሬግ ጎሳዎች የሚዋጥ አልነበረም።  ማሊ በ1960 ዓ.ም ነፃ ስትወጣ ይህ ህብረተሰብአዊ ቅራኔ ይባባሳል። የመጀመሪያው በታውሬጎች የተጠነሰስው ግጭት በ1960ዎች ውስጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በ1990ዎች ዓመታት መጀመሪያ ላይ ነው። ይሁንና ግን በ1992 ዓ.ም  ጠቡን ለማብረድና የስልጣን ክፍፍል ለማድረግ በመንግስትና በታውሬግ ተዋጊዎች መሀከል ስምምነት ቢደረግም፣ ስልጣኑን በጨበጠው የማሊ አገዛዝ  ስምምነቱ ተግባራዊ ለመሆን ባለመቻሉ በ2006 ዓ.ም እንደገና ጦርነቱ እንዲቀሰቀስ ተደረገ። ይህ እንደዚህ ሳለ ኮለኔል ጋዳፊ በፈረንሳይ መንግስት ቀስቃሽነትና መሪነት  በ2011 ዓ.ም ከስልጣን ሲወርዱና ሲገደሉ ሊቢያ ይኖሩ የነበሪ የታውሬግ ጎሳ ተወላጆች ወደ ማሊ በመመለስ ውስጥ ለሚካሄደው ትግል ውስጣዊ ኃይል ይሰጡታል። ብዙ መሳሪያዎችን ይዘው የሄዱ ስለነበሩ በቀላሉ ከማዕከላዊ የማሌ መንግስት ጋር ሊቋቋሙ  የሚያስችላቸው ነበር። በተለይም የኮሎኔል ጋዳፊ መገደልና የሊቢያ የውስጥ ፖለቲካ መለወጥ በአካባቢውና በማሊ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የበለጠ ያባብሰዋል። ኮለኔል ጋዳፊ ከመውደቃቸው በፊት ሁኔታው የተረጋጋና የተወሰኑ የታውሬግ ጎሳዎችም በሊቢያ ሚሊቴር ውስጥ የተካተቱ ስለነበሩ የኮሎኔል ጋዳፊ አገዛዝ በአካባቢው የተወሰነ ፀጥታን የማስፈን ኃይልና ተደማጭነትም ነበረው። ፈረንሳይና አሜሪካ በማንአልኝበት በኮለኔል ጋዳፊ ላይ ጦርነት በማወጃቸው ሰላምንና ዲሞክራሲን ያመጡ ሳይሆን ሁኔታው እንዲባባስና ለብዙ ሰዎች መሞት ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል።  በዚህ መልክ አዲስ ሁኔታ ሲፈጠር አዝዋርድ የሚባለው የጦር እንቅስቃሴ የስልጣንና የሀብት ክፍፍሉን ትግሉን በመተው ሙሉ ነፃነት ወይም መገንጠል ያስፈልጋል ወደሚለው ቀየረው። ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሄድና አዲስ የተጀመረውም እንቅስቃሴ ወደ ዘረፋነት ሲያመራ በዚህ የተደናገጠው የማሊ መንግስት ወታደር ልኮ ጦርነቱ ሲፋፋም፣ ሳላፊስት የሚባሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከታውሬግ የነፃነት እንቅስቃሴ ታጋዮች ጋር በማበር ትግሉን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲያመራ ያደርጉታል።  በተለይም ሊያድ አግ አግሃሊ የሚባለው የእስላም ሃይማኖት ተከታይ ስልጣኑን ሲያጠቃልል ቀደም ብሎ ከሃይማኖት ውጭ ይደረግ የነበረው የነፃነት እንቅስቃሴ መልኩን ይቀይራል። ይህ ሰው ቀድም ብሎ ስልጣን የነበረው ቢሆንም በአልጄሪያ የስለላ ድርጅት በመሰልጠንና በመጠምዘዝ የታውሬግን የነፃነት እንቅስቃሴ ከውስጥ ሆኖ እንዲያኮላሽ ለማድረግ በቃ። ምክንያቱም አልጄሪያ የታውሬጎችን መጠናከር ስለምትፈራ እኔንም ያስቸግሩኛል በማለት ከውስጥ ሆኖ ለነፃነት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያኮላሽላት ሰው አሰርጋ አስገባች። በዚህ መልክ ጠቅላላው የፖለቲካ ስልት ይቀየራል።  በሊያድ አግሃሊ የሚመራው የእስልምና እንቅስቃሴ ይባስ ብሎ አንሳር አድ ዲን ከሚባለው ሌላ አክራሪ የእስልምና እንቅስቃሴ ጋር አንድነትን በመመስረት ሁኔታውን ያባብሱታል።

ይህ በሊቢያ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታና፣ በተጨማሪም የአልጄሪያ የስለላ ድርጅት ለዚህ ዐይነቱ አክራሪ የእስልምና ሃይማኖት እንቅስቃሴ ማንኛውንም ድጋፍ በመስጠቱና በጦርነቱ እንዲገፋበት በማድረጉ አካባቢው የእስላም አክራሪ ኃይሎችና አሸባሪዎች የሚንቀሳቀሱበት በመሆኑ የግዴታ ጣልቃ መግባት ያስፈልጋል ለሚለው የአሜሪካንና የፈረንሳይ መንግስት አመቺ ሁኔታ ፈጠረላቸው።  የአሜሪካና የአልጄሪያ የስለላ ድርጅቶች አንድ ላይ መተጋገዝም ለሁኔታው መባባስ ልዩ ዕምርታ ይሰጡታል። ይህ አዲስ የተፈጠረው ሁኔታ በተለይም አሜሪካኖች የቻይናን በተለያዩ አገሮች ጣልቃ መግባትና የጥሬ-ሀብት ተቀራማች መሆናቸውን ለመቋቋምና አካባቢውን ለማመስ የሚያመቻቸው ሆነላቸው።

ባጭሩ  በአፍርኮምና(AFRICOM) በፈረንሳይ፣ እንዲሁም በጀርመን አሸባሪና አክራሪ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለመዋጋት ተብሎ በማሊ በረሃና በኒጀር የሚካሄደው ጦርነት ራሳቸው የስለላ ድርጅቶች ለሁኔታው ልዩ ዕምርታ በመስጠት የማሊና የኒጀር መንግስት ሊወጡ የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ከተዋቸዋል። በተለይም የአፍሪኮም ዋናው ተግባር አሸባሪዎችንና አክራሪ ኃይሎችን መዋጋት በሚለው ሽፋን ስር ከጀርመንና ከፈረንሳይ የመከላከያ ስራዊት ጋር በመሆን ጦርነቱን ሪጂናዊና ቀስ በቀስም በጠቅላላው አፍሪካ ውስጥ ማዳረስ ወይም አህጉራዊ ማድረግ ነው። ጦርነቱ የአሜሪካና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ብቻ እንዳይመስል ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ መኮንኖች ልዩ ስልጠና በመውሰድ አካባቢውንና አህጉሩን በማመስና ሰላም በማደፍረስ የአህጉሩን ህዝብ ታሪክ እያበላሹና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዳይመጣ እያደረጉ ነው። 53  የአፍሪካ አገሮች የአፍሪኮም አባሎች ሲሆኑ፣.  ዋናው መቀመጫው ሽቱትጋርት(Stuttgart) የሚባል በደቡብ ጀርመን የሚገኝ ትልቅ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ ጂቡቲም አላቸው።

ከዚህ ስንነሳ  አሸባሪዎችን ለመዋጋት እየተባለ የሚደረገው ጣልቃ ገብነትና ጦርነትን በየቦታው መለኮስ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ርስ በርሱ እንዲዋጋ በማድረግ ሁኔታውን የሚያባብስ እንጂ ጋብ የሚያደርገው አይደለም። በእንደዚህ ዐይነቱ ጣልቃ ገብነትም አሸባሪዎች የሚያካሂዱትን ጦርነት ለማብረድ ወይም ለማቆም በፍጹም አይቻልም። ሁኔታው ይበልጥ ለአዳዲስ ታጋዮችና፣ የአሜሪካንና የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ የባለይነትን ለሚጠሉ መሳሪያ እያነሱ እንዲዋጉ ያበረታታቸዋል። የአሜሪካንም ዋናው ፍላጎትና ዓላማ ይህ ነው። ሰላምን ማስፈን ሳይሆን ጦርነትን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ማድረግ ነው። በዚህ መልክ ብቻ ነው የበላይነቱን ይዞ ሊቆይ ይችላል ብሎ የሚያስበው። ስለሆነም የፈረንሳይ እንዲሁም የጀርመን መንግስታት በጦርነቱ ውስጥ መካተት  በዚያ አካባቢ ሰላምን ለማስፈን ሳይሆን የቻይናዎችን ግፊት ለመግታት ብቻ ነው። በዚያውም መጠንም ከረጅም ጊዜ አንፃር ሰላም እንዳይኖርና ህዝቦች ነፃነታቸውን እንዳይቀዳጁ የሚደረግ ስትራቴጂ ነው። ጦርነቱ የጥሬ-ሃብትን ለመቆጣጠር የሚደረግ አዲስ የቅኝ አገዛዝ ስልት ነው። የአፍርኮምም ዋናው ተግባር ይህ ነው። በተለይም ሰፋ ያለ የጥሬ -ሃብት ክምችት ያላቸውን አገሮች ማመስና ሰላም አሳጥቶ የጥሬ-ሃብታቸውን  በቁጥጥር ስር ማድረግና መዝረፍ ነው።

ወደ ኢራክና ሶሪያ ከመሄዳችን በፊት የሊቢያን ሁኔታ በአጭሩ እንመለክት። በመጀመሪያ ደረጃ ኮሎኔል ጋዳፊ አምባገነን ለመሆናቸው የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ይህ ጉዳይ ደግሞ ከሊቢያ የህብረተሰብ አውቃቀር ጋር የተያያዘ ሲሆን  ምዕራቦች እንደሚመኙት በቀላሉ ወደ ሊበራል ዲሞክራሲና ወደ ገበያ ኢኮኖሚ የሚለወጥ አይደለም። ይሁንና ግን የሊቢያ ህዝብ በኮሎኔል ጋዳፊ ዘመን የምዕራቡ ዐይነት የሊበራል ዲሞክራሲ ከማጣቱ በስተቀር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በትምህርትና በህክምና እንዲሁም በቤት ችግር የሚሰቃይ አይደለም። ኮሎኔል ጋዳፊ ከዘይት ሺያጭ ያገኙ የነበረውን ገንዝብ በሊቢያ ህዝብ ስም የሚያስቀምጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ በተቻለ መጠን ኢኮኖሚው እንዲያድግ አስፈላጊውን የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ የሚያካሂዱ ነበሩ። በተጨማሪም ትምህርት ነፃ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ አገር ሄዶ የሚማር ተማሪ በወር እስከ ሁለት ሺህ ዶላር ይቆረጥለት ነበር። በእረፍት ጊዜም በተለይም ምስራቅ አውሮፓ የሚማሩ የሊቢያ ዜጎች አውሮፕላን ተልኮላቸው ወደ አገራቸው ተመልሰው እረፈት የማድረግ ዕድል ነበራቸው። ወጪውንም የሚሸፍነው መንግስት ነው። እያንዳንዱ ተማሪ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ አገሩ ሲመለስ ስራ እስኪያገኝ ድረስ ሙሉ ደሞዝ ይከፈለዋል። ስራ ይዞ ትዳር ሲመሰርት ደግሞ ለመቋቋሚያ ተብሎ እስከ ሰላሳ ሺህ ዶላር ድረስ ይሰጠዋል። የራሳቸውን ንግድ ወይም ኢንቬስትሜንት ለማካሄድ ለሚፈልጉ ደግሞ ድጎማና በቅናሽ ወለድ ብድር ይሰጣቸው ነበር። ለሚያርሰውም ገበሬ እንዲዚሁ በሬና መሬት ወይም ሌላ የማረሻ መሳሪያ ተገዝቶ ይሰጠው ነበር። ይህ ዐይነቱ ድጋፋ የምዕራቦችን የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ የገበያ አስተሳሰብና „እሴት“ የሚፃረር ነው። ስለሆነም በእነሱ ዕይታ እንደዚህ ዐይነቱ የምዕራቡን ሞዴል የሚፃረር ከምድረ-ገጽ መጥፋት አለበት። የኮሎኔል ጋዳፊ „ወንጄል“ ይህ ብቻ አልነበረም።  ሰውየው በአፍሪካ ውስጥ ተደማጭነት እንዲኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካ ራሱን እንዲችል የሚጥሩ መሪ ነበሩ። ስለሆነም በአፍሪካ ውስጥ የኢንዱስትሪ አብዮት መካሄድ አለበት፤ በዚህ ብቻ ነው አህጉሩ የሚከበረው ብለው የሚያምኑ መሪ ነበሩ። በመሆኑም ይህንን ህልማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ አፍሪካ ራሱን የቻለ አንድ ከረንሲ እንደሚያስፈልገውና፣ ይህም ገንዘብ በወርቅ ላይ የተመረኮዘ ዲናር ጎልድ ተብሎ የሚጠራና፣ ኦይሮንና ዶላርን የሚፎካከር መሆኑን ያበስራል። ይህንን ወሬ የሰሙ የአሜሪካንና የፈረንሳይ መንግስት፣ እንዲሁም እንግሊዝ እንዴት አድርገው ኮሎኔል ጋዳፊን እንደሚጥሉና የሊቢያን ሀብት እንደሚዘርፉ ያውጠነጥናሉ። የመጨረሻ መጨረሻም አሜሪካኖች ያሰለጠኗቸውን የሲአይ ኤ ሰዎች አሾልከው በማስገባት ረብሻ እንዲጀመር ያደርጋሉ። በመቀጠልም በጉልበት ሰተት ብለው በመግባት በአውሮፕላን በመደብደብ የኮሎኔል ጋዳፊን መንግስት ይጥሉታል። በዚህ ዐይነቱ ዐይን ያወጣ ወንጀልና ውንብድና ዛሬ ሊቢያ ውስጥ የሊቢያን ህዝብ የሚወክል መንግስት እንዳይኖር ተደርጓል። አሜሪካኖች ያሰለጠኗቸው የእስላም አክራሪዎች ሰርገው በመግባት በተለያየ አቅጣጫ አገሪቱን እያመሱ ነው።  በሊቢያ ውስጥ ህዝቡን የሚወክልና ውጭ የተከማቸውን ሀብት የሚቆጣጠር መንግስ ባለመኖሩ ኮሎኔል ጋዳፊ በሊቢያ ህዝብ ስም ውጭ አገር ባንኮች ያስቀመጡትን ከሁለት መቶ ሃምሳ ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥና የወርቅ ክምች ሊቀልጥ ችሏል።አሜሪካና የተቀሩት የአውሮፓ መንግስታት ዘርፈውታል።  እንግዲህ ይህ ነው ሞራል፣ ስነ-ምግባር፣ የዲሞክራሲና የሊበራል ኢኮኖሚ እሴት አለኝ የሚለው የምዕራቡ ዓለምና በተለይም የአሜሪካ ተግባር።

ወደ ኢራክና ወደ ሶርያ እንምጣ። በመጀመሪያ አሜሪካን የሚባል አገር ከመፈጠሩና ከመታወቁ በፊት ኢራክና ሶርያ ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ የሚቆጠር ስልጣኔ የነበራቸው ናቸው። የማቲማቲክስና የሌሎች ሳይንስ ግኝት ምንጮች ናቸው። ሁለቱ አገሮች ከግብጽ ስልጣኔ ጋር ተደምሮ ለምዕራቡ ስልጣኔ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝብ ታላቅ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ናቸው። ግሪኮች ዕውቀታቸውንና ፍልስፍናቸውን ከዚያ በመማርና በመቅዳት ነው ልዩ ዕምርታ በመሰጠት ለዘመኑ ስልጣኔ መሰረት መጣል የቻሉት። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ እነዚህ የስልጣኔ ምንጭ የሆኑ አገሮች መከበር ያለባቸውና ልዩ እንክብካቤም የሚያስፈልጋቸው ነበሩ። ልክ ለምን ስልጣኔን አሳያችሁን ብሎ እንደሚናደድ ሰውና አገር የነጩ ኦሊጋርኪ መደብ ያለ የሌለውን ኃይል በመሰብሰብና በውሸት በመወንጀል፣ በተለይም ሁለቱ አገሮች ዛሬ የምናየው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁ ተደርገዋል። የጥንት ከተማዎቻቸው ፈርሰውባቸዋል። በሺህ የሚቆጠሩ የታሪክ ቅርሶች ወድመውባቸዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ መጽሀፎች ተዘርፈዋል፤ አንዳንዶችም ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል። በአጭሩ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው አመጸኛ ኃይል መንግስት ያለው የሌለውን ኃይል በማስተባበር የታሪክ ቅርስን አውድሟል። ይህ አሳዛኝ ሁኔታና ወንጀል ነው ለእስላሙ መንግስት(Islamic State) መነሾ የሆነው።

በእነዚህ አገሮች አይሲስ የሚባለው አክራሪ የእስልምና እንቅስቃሴ የተጀመረው የሳዳም ሁሴን መንግስት ከፈረሰና ሺይቶች ስልጣንን ጠቅልለው ከወሰዱ በኋላ ነው።በመጀመሪያ አሜሪካኖች በኢራክና በኢራን መሀከል ጦርነት እንዲካሄድ በመገፋፋት የሳዳም ሁሴንን መንግስት አስፈላጊውን መሳሪያ በሙሉ ያስታጥቁታል። በሁለቱ አገሮች መሀከል በተካሄደው ጦርነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱና ሲቆስሉ፣ ጦርነቱ በአጠቃላይ ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል። ሳዳም ከጦርነቱ ሲላቀቅ በመሳሪያ ቢታጠቅም ኢኮኖሚው በጣም ተዳክሞ ነበር። በዚህ ወቅት ነው ኩዌት ብዙ ዘይት በማምረት የዓለምን ገበያ ማጥለቅለቅ የጀመረችው። ይህ ሁኔታ በእኮኖሚ ለተዳከመው የሳዳም ሁሴን መንግስት የሚዋጥለት አልነበረም። ይህ በዚህ እንዳለ የሳዳም ሁሴን መንግስት ኩዌትን ለመውረር ዝግጅት ያደርጋል። በጊዜው ኢራክ የነበረችው የአሜሪካ መንግስት አምባሳደር በወረራው ችግር አንደሌለባት የአረንጓዴ መብራት ትሰጠዋለች። ይህ ሁኔታ ግን ሳዳምን ወጥመድ ውስጥ የሚከተው ነበር። አሁን አሜሪካኖች ወረራውን አሳበው ኢራክን የሚወሩበትና ሳዳምን የሚያባርሩበት ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል። ይህ የአሜሪካኖች ስትራቴጂ ደግሞ እስራኤልን በአካባቢው ብቸኛዋ ኃያል መንግስት ሆና እንድትወጣ ታስቦ የታቀደ በመሆኑ አመቺ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ሳዳምም ኩዌትን ለቆ ከወጣ በኋላ የአቶም ቦምብ ለመስራት ዝግጅት ላይ ነህ በማለት የውሽት ክስ በማካሄድ ማዕቀብ ያደርጉበታል። ጠቅላላውን ሁኔታ ሳዳምን ለማባረርና ኢራክን ለሶስት ለመከፋፈል ይጠቀሙበታል። የሳዳም መንግስት ሲፈራርስ የሱኒቶች ኃይል እንዳለ ይዳከማል፤ ይበታተናልምም።  ቀደም ብለው ስልጣንን የሚቆጣጠሩት የሱኒት ሃይማኖት ተከታዮች ቦታ ባለማግኘታቸውና ሳዳም ሁሴን የገነባውም የጸጥታና የሚሊታሪ ኃይል በመፈረካከሱ ለአክራሪ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። በ2011 ዓ.ም በሶሪያ ደግሞ አዲስ ሁኔታ ሲፈጠር፣ ሲአይ ኤ፣ የሳውዲ አረብያ መንግስት፣ እስራኤል፣ የቱርክ የስለላ ድርጅትና ሚሊታሪ፣ በጫሩ ጠቅላላው ስለጠንኩኝ የሚለው የምዕራቡ ዓለም አክራሪ ኃይሎችን እያሰለጠነ ያስገባል።  በተለይም በምዕራቡ የስለላ ድርጅት እየተመለመሉ ከአሜሪካን፣ ከፈረንሳይ፣  ከእንግሊዝና ከጀርመን የገቡ የእነዚህ አገር ፓስፓርት ያላቸው  የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ነበሩ። አብዛኛዎቹ ወጣት ሲሆኑ በቀላሉ በገንዘብ የሚታለሉና ዕውነተኛውን ዓለም በዚህች ምድር ላይ ሳይሆን ሰማይ ላይ የሚያገኙ የሚመስላቸው ነበሩ። በዚህ ዐይነቱ ዐይን ያወጣ ተንኮል የፕሬዚደንት አሳድን መንግስት ወጥመድ ውስጥ በመክተት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ህይወቱን እንዲያጣ አድርገዋል።  ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሶሪያኖች ደግሞ እንዲሰደዱ ተደርገዋል። ይህ ሁሉ የተደረገው ከካታርና ክሳውዲ አረብያ በመነሳት በሶርያ በርሃ ውስጥ አቆራርጦ የጋዝ ቱቦ ለመዝርጋትና ጋዝ ወደ አውሮፓ ለማምጣት የተተለመ እጅግ አደገኛ ስትራቴጅ ነበር። በዚህ አማካይነት ምዕራብ አውሮፓን ከራሺያ የጋዝ ጥገኝነት ለማላቀቅና ኢኮኖሚያውንም ለማዳከም ነበር ዋናው ዓላማው። ይሁንና ግን በራሺያ ጣልቃ ገብነት አሜሪካኖችም ሆኑ የተቀረው  የምዕራቡ ዓለም ያሰቡት ህልምና የሰሩት ተንኮል የመጨረሻ መጨረሻ ግቡን ሊመታ አልቻለም። ራሺያ፣ ኢራንና የሊባኖኑ ሂስቦላ ባይኖሩና ለዕርዳታም ባይደርሱ ኖር የአሳድ መንግስት አልቆለት ነበር።

ያም ሆነ ይህ በዚህ ዐይነቱ የምዕራቡ ወንጀል የተወሰነው የዋሁ ሶሪያዊ መታለሉ ብቻ ሳይሆን የራሱንም የታሪክ ቅርስ እንዲያወድም ሊያደርግ በቅቷል። ራሱ ሳያውቀ አሌፖንና ፔልሜራን የመሳሰሉ ታሪካዊ ቦታዎችና መገበያያዎች እንዳሉ እንዲወድሙ ተደርገዋል። ከጦርነቱ በፊት ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የኢራክም ሆነ የሶሪያ ህዝቦች በድህነት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ አልነበሩም። የሳድምም ሆነ የፕሬዚደንት አሳድ መንግስት ህዝቡ እንዲማርና እንዲያውቅ ይገፋፉና ኢንቬስትም ያደርጉ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም በሶርያ የተማረው ምሁር በተወሳሰበ መልክ የሚያስብና በጣምም የሰለጠነ ነው። በዚህ መልክ በሁለቱ አገሮች ማዕከለኛ ከበርቴ ወይም የነቃ ሚድል ክላስ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል በማደግ ላይ ነበር። በሁለቱም አገሮች፣ በተለይም በሶሪያ የተለያየ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ጎሳዎችም በስምምነት የሚኖሩባት አገር ነበረች። ሶሪያም ለቱሪዝም የምታመች አገር ነበረች። በውሽት ጦርነት የተነሳ ይህ ዐይነቱ ህይወትና ዕውቀት ነው እንዲወድም የተደረገው።

ይህን የመሰለውን ወንጀል አስመልክቶ በቅርቡ አንድ ዲሚትሪ ተብሎ የሚጠራ አርዕስት ያለው ድራማ በፍሪድሪክ ሺለር የተጻፈና በጀርመን የቲያትር ደራሲዎች አቀነባባሪነትና ትግሉን ጥለው በወጡና እዚህ ጀርመን ጥገኝነት ጠይቀው በሚኖሩ  ሶሪያውያን የተሰራ ቲያትር አለ። ድራማው ራሽያ ከ1598-1613 ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻና የረሃብ ዘመን ውስጥ የነበረችበትን ሁኔታ አስመልክቶ የተጻፈ ነው። ዋናው ይዘቱም በጊዜው  እኔ ነኝ ዕውነተኛው ዛር፣ ስልጣን ላይ  ያለው ዕውነተኛው ዛር አይደለም፣ ስልጣንም የሚገባኝ እኔ ነኝ በማለት ፖላንድ ክራካው የሚባል ከተማ ይገዙ የነበሩ መሳፍንት ጋ ሄዶ ዲሚትሪ በመባል የሚታወቅ እራሱን ያስተዋውቃል። መሳፍንቶችና ልዑሎችን በማሳመን እሱ ትክክለኛው መሆኑን ያረጋግጡለታል።  ስለሆነም እንዲያስታጥቁትና ጦርነትም ገጥሞ ስልጣንን በኃይል ለመወሰድ እንደሚፈልግና የዕውነተኛው ዛርን፣ በጊዜው ኢቫን አረመኔው በመባል የሚታወቀውን ንጉስ ዝናን ለመመለስ እንደሚፈልግ ይነግራቸዋል። የድራማው ዋና መልዕክት በሀሰት ላይ በተመሰረተ ክስ ወይም ወሬ  በሁለት አገሮች መሀከል  ጦርነት እንደሚነሳና፣  ከቀድሞው የባሰ ምስቅቅልቅል ሁኔታ እንደሚፈጠር ለማመልከት የተደረሰ ዕውነት አዘል ድራማ ነው። ስለሆነም የቲያትሩ ተዋንያን የሆኑ ሶሪያውያን በተለይም በሲአይ ኤ እየተመለመሉ፣ በተለይም መንግስት ነክ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅት ነን ባዮች እንዳታለሏቸውና ጦርነት እንዲቀሰቅሱ ምክንያት እንደሆናቸው ነው። ስለሆነም እነዚህ ሶርያውያን በተመለመሉበትና ጦርነት በሚያካሄዱበት ጊዜ ትላልቅ ጂፕ መኪናዎች እንደሚሰጣቸውና፣ በቡዙ ሺህ የሚቆጠር ዶላርም እንደሚከፈላቸውና  ጦርነቱን ያካሄዱ እንደነበር ነው። ይሁንና ግን የመጨረሻ መጨረሻ ነገሩ የማያዋጣ መስሎ ሲታያቸውና ነገሩም ሲገባቸው አምልጠው ወደ ጀርመን ይመጣሉ። ያደረሱትን ጉዳትና የደረሰባቸውን ስቃይ ሁሉ ይናገራሉ። ተታለውም እንደ ሆልምስ የመሳሰሉ ትላልቅ ታሪካዊና የንግድ ከተማዎችን ድምጥማጣቸው እንዲጠፉ አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ በድራማ መልክ ያቀርባሉ። ይህ ድራማ በዕውነተኛ ድርጊት ላይ ተመርኩዞ የተሰራ ድራማ ሲሆን፣ በተለይም ሲአይ ኤ የሰራውንና የሚሰራውን ወንጀል የሚያጋልጥ ነው።  እንግዲህ የምዕራቡ ውስብስብ ተንኮልና ታሪክን አውዳሚነት ይህንን ነው የሚመሰለው።

ከዚህ አጠር መጠን ብሎ ከቀረበው ሀተታ ስንነሳ ሻለቃ ዳዊት ሊያያቸው፣ ሊገነዘባቸውና ጭንቅላቱ ውስጥ አግብቶ ሊያብላላቸው  የሚገቡና በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን በፍጹም ቁጥር ውስጥ አላስገባም። በእሱ ዕምነት ዛሬ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በማዕከለኛው ምስራቅ አረብ አገሮችና በሊቢያም የሚካሄዱት ጦርነቶች ዝም ብሎ በጭፍን በእስላም አክራሪ ኃይሎች የሚካሄዱ ጦርነቶች ናቸው። የአሜሪካን መንግስትና የስለላ ድርጅቱ፣ እንዲሁም የተቀሩት የምዕራብ የስለላ ድርጅቶች የጸነሷቸውና ያፋፋሟቸው ሳይሆኑ፣ አክራሪ ኃይሎች ብቻ ናቸው የሚለን። የሱ ግምገማ፣ ግምገማ ካልነው በቡዙ ሺህ ወረቀቶች ተጠናቅረው የወጡ ሀቀኛ ጥናቶችን ብቻ ሳይሆን፣ በምድር ላይ ያለውን ሀቅ የሚፃረርና ለመቀበልም የማይፈልግ ነው። በዚህ ዐይነት አመለካከቱና አጻጻፉ ከማን ጋር እንደቆመም አረጋግጦልናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘረጋው ዓለምን ከሚያዋክበውና የሰውን ልጅ መግቢያና መውጫ ካሳጣው የአገዛዝ፣ የጭቆናና የጦርነት ሰንሰለት ውስጥ የገባ ስለሆነ ከማን ጋር እንደቆመ በዚህ ጽሁፉ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ጽሁፎቹ አረጋግጦልናል። አቀራረቡ እጅግ አሳሳችና አደገኛ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለምን ህዝብ ሰላም ፈላጊነትና የስልጣኔን ምኞት የሚጻረር ነው። የዓለም ህዝብ የሚፈልገው ጦርነትት ሳይሆን ሰላምንና ስልጣኔን ብቻ ነው። በዓለም ታሪክ ውስጥ የሚከሰቱና ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች ዕልቂት ምክንያት የሚሆኑ ጦርነቶች የሚታቀዱትና የሚቀሰቀሱት በተራ ወይም በደሃ ሰዎች አይደለም። የጦርነት ምንጮች ሁልጊዜ ስልጣንን የተቆናጠጡና ሲጠግቡ የሚያደርጉትን በሚያጡ፣ ውስጥ የተደበቀ ፍላጎታቸውን ሊያሟሉ የሚችሉት ጦርነት ቀስቅሰው ተራ ሰው ሲያልቅ ብቻ  በሚደሰቱ ሰዎች ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ  ማንኛውም እንዲያውቀው የሚገባ ነገር፣ ይህ ዐይነቱ በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም በአፍሪካና በሌሎች አገሮች የሚካሄደው ጦርነት የጥሬ-ሀብትን ለመቀራመት ብቻ ሳይሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የአፍሪካንና የአረብን ህዝብ ቁጥር ለመቀነስም ነው። ማንኛውም ጤና ጭንቅላት ያለው ሰው የዚህ ዐይነቱ ወንጀል ተባባሪ መሆን የለበትም። እንደዚህ ዐይነቱን በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የተቀነባበረውንና ወደፊትም የሚቀነባበረውን ጦርነት ማጋለጥና መዋጋት ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ነው።  ለጊዜው የበላይነትን ተቀዳጅተናል፣ የዓለምን ህዝብ ዕድል እኛ ብቻ ነን ለመወሰን የምንችለው ብለው በተነሱና፣ የሚሊታሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይል አለን ብለው ዓለምን የሚያተረማምሱ ጥቂት አገሮችን ዝም ብለን ማየት ያለብን አይመስለኝም።

   ዓለም አቀፋዊ ጦርነት የካፒታሊዝም ዋናው አካል ነው !

እስከ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ድረስ  የተካሄዱትን ትላልቅ  ጦርነቶች በምንመረምርበት ጊዜ ጦርነቶቹ በሙሉ በአውሮፓ ምድር ነው የተካሄዱት። አንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ብቻ ስንመለከት በራሺያ በኋላ ደግሞ በሶቭየት ህብረት ላይ ያነጠጣሩ ነበሩ። የሁለቱም ጦርነቶች ዋና ዓላማ ራሺያ  ጠንካራና ኃያል አገርና መንግስት ሆና እንዳትወጣና ተፎካካሪ እንዳትሆን ታስቦ የተካሄዱ ጦርነቶች ናቸው። በተለይም ሂትለር በሶቭየት ህብረት ላይ ካነጣጠረው  ጦር በስተጀርባ አሜሪካና እንግሊዝ እንደነበሩበት የታወቀ ጉዳይ ነው። ዋና ዓላማውም ሶቭየት ህብረትን በቦንብ ደብድቦ እንደገና እንዳታንሰራራ ለማድረግ ነበር።  ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላም ከአውሮፓ ውጭ የተካሄዱትን ጦርነቶችና ዛሬም በተለያዩ አገሮች በሃይማኖትና በጎሳ ስም ተሳበው የሚካሄዱትን ጦርነቶች ስንመለከት ከጦርነቶቹ በስተጀርባ የአሜሪካን፣ የእንግሊዝና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅቶች እንዳሉበት መረጃዎች ያረጋግጣሉ።  ባጭሩ እነዚህ ጦርነቶች በሙሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካንና በእንግሊዝ ቀጥሎም በፈረንሳይ አገዛዞች የሚቀሰቀሱና የሚካሄዱ ጦርነቶች ናቸው። ይህም ማለት ባለፉት ሰባ ዓመታት የተለያየ ምክንያት እየተሰጣቸው የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ውጭ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ ብራዚል፣ አርጀንቲናና ቺሌ እንዲሁም በተቀሩት የላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካን አገሮች ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ፣ በተለይም  ከ1960 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ብቅ ያሉት አምባገነናዊና ፋሺሽታዊ አገዛዞች ከምዕራብ አውሮፓው፣ በተለይም ከአሜሪካን ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም ጋር በጥብቅ የተያዙ ናቸው። ኮሙኒዝምን ለመዋጋት ተብሎ ላይ በተጠቀሱት መንግስታት አማካይነት በተማረው ህዝብ ላይ የተካሄዱት አፈናዎችና ግድያዎች ዋና ዓላማው በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጠንካራና በራሱ የሚተማመን፣ እንዲሁም ፈጣሪ የሆነ የማዕከለኛ ከበርቴ ወይም ሚድል ክላስ እንዳያንሰራራና እንዳይዳብር ለማድረግ ታስቦ ነው። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ይህን ዐይነቱን የተወሳሰበ ሁኔታ ለማውጠንጠን ጊዜ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣  ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚነሱትን ጦርነቶች በሙሉ እንደተፈጥሮአዊ አድርጎ መውሰድና ግንዛቤ ውስጥ ለማስገባት አለመቻል ነው። ሀቁ ግን ጦርነቶች በሙሉ የበላይነት መግለጫዎና ማረጋገጫዎች ናቸው። በተለይም ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ጦርነት አንደኛው  የካፒታሊዝም ውስጣዊ ህግና መለያ በመሆን በተለያዩ አገሮች ጥቅምን ማስጠበቂያ መሳሪያ ለመሆን በቅቷል።  ስለሆነም ካፒታሊዝም ካለጦርነት በፍጹም ሊኖር አይችልም። ጦርነት የካፒታሊዝም አንዱ አካልና ውስጣዊ ህግ በመሆኑ ደካማ አገሮችን የራሱ ተቀጥያ እያደረገና፣ በየመንግስታት መኪና ውስጥም ሰርጎ በመግባት ደካማ አገሮችን ወደ ጦርነት አውድማ ይለውጣቸዋል። ይህ በማይቻልበት ቦታ ደግሞ አሸባሪዎችን በፈንጂ እያስታጠቀ በከተማዎች ውስጥ፣ በተለይም ስትራቴጂክ በሆኑ ቦታዎች ላይ ቦንብ በማፈንዳት ህዝብ እየተረበሸና እየተደናገጠ እንዲኖር ያደርጋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነቱ እያጣ በመጣበት ዘመን ያለው አማራጭ በሁሉም አቅጣጫ በድብቅና በይፋ በየዋህ ህዝቦች ላይ ጦርነት ማወጅ ነው። በዚህ ዐይነቱ ጦርነትና አገሮችን ማከረባበት ብቻ ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነቱን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት የሚችለው። ሎጂኩ ቀላል ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የህግ የበላይነት ሰፈነ ቢባልም የየአገሮችን ህልውና የሚወስነው የመንግስትን መኪና የጨበጡ ሳይሆኑ ራሱ ስርዓቱ እንዳለ ነው። ካፒታሊዝም የአንድን ህብረተሰብ ደህንነትና ብልጽግና ለመጠበቅ ተብሎ የተቋቋመ ስርዓት ሳይሆን፣ ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ በአሸናፊነት የወጣና ጠቅላላውን ህብረተሰብ ማቀፍ የቻለና፣ የጠቅላላውንም ህብረተሰብ ዕድል ወሳኝ የሆነ ስርዓት ነው። ዋናው ዓላማውም በተለያየ መልክ የሚገለጸውን የሰውን የፍጆታ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን፣ የካፒታሊዝም ስልተምርት የምርት ክንዋኔ ዋና ዓላማ አምርቶ ትርፍ ለማግኝት ብቻ ነው። ማንኛውም ካፒታሊስት በምርት ሂደት ውስጥ እሳተፋለሁ ብሎ ሲነሳ ከዚህ ስሌት በመነሳት ነው። ስለዚህም የገበያ ሁኔታዎችን፣ በገበያ ላይ ተመርተው የሚቀርቡ ምርቶችንና የጥሬ-ሀብት አቅርቦትንና ሊሰራ የሚችል የሰው ኃይልን በሚገባ ካጠና በኋላ በምርት ሂደት ውስጥ ይሳተፋል። ይሁንና ሁሉም ካፒታሊስቶች ተመሳሳይ ቅድመ-ሁኔታዎችና አካሄድ ስለማይኖራቸው የተወሰነው ከገበያ እየተስፈናጠረ ሲወጣ፣ የቀረው ደግሞ የምርት ክንውንን በመቆጣጠርና በማበጥ፣ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቆላለፍ እየሰፋና እያደገ ይመጣል። ይህ ዐይነቱ ሂደት ለትላልቅ ኩባንያዎችና የጥሬ-ሀብትን ለሚቆጣጠሩ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መንገዱን ይከፍታል። ከዚህ ስንነሳ በተለያዩ አገሮች ያሉትን የየመንገስታት ዕድል ወሳኞች ተደራጀተው የሚገኙ ባንኮችና፣ በየመስሪያቤቱና በየፓርሊያሜንቱ ፊት ለፊት ቢሮ ከፍተው ህግ አውጭዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ናቸው። የሚወጡትም ህጎች ከዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ግኑኝነት ጋር በመተሳሰር ነው። ስለዚህም በካፒታሊስት አገሮች ያሉ መንግስታት በሙሉ የትላልቅ ኩባንያዎችን፣ የባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጥቅም አስጠባቂዎች ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ ይህን ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትና በዚህ ላይ የተመሰረተውን የምርት ሂደትና የትርፍ ትርፍ ማካበት ክንዋኔ ለመጠበቅ ነው። ይህን አጠቃላዩን ስዕል ትተን ወደ ጦር መሳሪያ ምርት ላይ ብቻ እናተኩር።

እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ የጦር መሳሪያዎች፣ የኬሚካል፣ የባይሎጂና የአቶም ቦምብም ጨምሮ የሚመረቱት የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችና አሜሪካን ነው። በተለይም ስትራቴጅክ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን የሚገዙት ራሳቸው የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት ናቸው። ለምሳሌ የትረምፕ አስተዳደር በአሁኑ ዐመት ባጀቱ $ 700  ቢሊዮን ዶላር ለመከላከያ ወጪ መድቧል። በሌላ ወገን ደግሞ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል በጣም አስፈላጊ የሆኑ ለህክምናና ለሌሎች የማህበራዊ ወጪ የተመደቡ በጀቶችን ቀንሷል፤ ወይም ለመቀነስ እየጣረ ነው። ስልሆነም መንግስት የጦር መሳሪያ ምርትን የሚቆጣጠሩና ባለቤትም የሆኑ ባለሀብታሞችን በሀብታቸው ላይ ሀብት ይጨምርላቸዋል።  የጦር መሳሪያ ምርት  ራሱን የቻለ ቴክኖሎጂ በመሆኑና  ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች  የስራ ዕድልም የሚከፍት ስለሆነና፣ ኢንዱስትሪውም ከተለያዩ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር የተያያዘ በመሆኑ አንደኛው የካፒታሊዝም የሀብት ክምችት መሰረት ነው። የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዎችን የሚቆጣጠሩ ትላልቅ ባለሀብታሞችና ባለቤቶች ደግሞ በብዙ ሺህ ድር ከሚሊታሪውና ከስለላ ድርጅቶች ጋር የተቆላለፉ በመሆናቸው የትርፍ ትርፍ ሊያካብቱ የሚችሉት የግዴታ የጦር መሳሪያዎች በተከታታይ ሲመረቱና በተለያዩ አገሮች ሲሸጡና በዚያው መጠንም ጦርነት ሲካሄድ ብቻ ነው። የስለላ ደርጅቶችና የጄኔራሎች ዋና ተግባር ደግሞ በየጊዜው አዳዲስ ቦታዎች እየፈለጉና ምክንያት እየፈጠሩ ጦርነት ማካሄድ ነው። የእነሱ  በማዕረግ ማደግም በጥብቅ ከጦርነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ማንም አገር ሳይወራቸው በውሸት ክስ አንድን አገር በመውንጀልና አንዳንድ የአገሪውን ሰው ካታለሉና ጦርነት ከቀሰቀሱ በኋላ ቀስ በቀስ ሁኔታው ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዲያመራ  ያደርጋሉ። በዚህ አማካይነት በአንድ ጊዜ ብዙ ግቦችን ይመታሉ። የጥሬ ሀብትን ለመቆጣጠር ይችላሉ። የጦር ማሳሪያዎችን ያራግፋሉ። የሶስተኛው ዓለም አገሮችን የመንግስት መኪናዎች የባሰውኑ ጦረኛ እንዲሆኑ በመገፋፋት ወደ ውስጥ መንግስታት መስራት የሚገባቸውን ነገሮች እንዳይሰሩ ያግዷቸዋል። በዚህ ዐይነቱ የተቆላለፈ ሁኔታ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች የትርፍ ትርፍ ያካብታሉ። አገሮች የአዳዲስ መሳሪያዎች መለማመጃ በመሆን ምስኪን ህዝብ ህይወቱን እንዲያጣ ይደረጋል። በዚያው መጠንም በየአገሮች ውስጥ በሚነሳውና በሚቀሰቀሰው ጦርነት የአሜሪካንና የእንግሊዝ መኮንኖች የጄኔራልነት ማዕረግ እንዲቀዳጁ ይደረጋል። ባጭሩ ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ምስኪንን ህዝብ የሚጨርሰው ጦርነት የክርስትናን ሃይማኖት ተቀብያለሁ፣ ጠበቃውም ነኝ፣ ከእግዚአብሄርም የተሰጠኝ ፈቃድና ሰለጠንኩኝ ከሚለው የምዕራቡ ካፒታሊዝምና በአሜሪካን አማካይነት ነው። ከዚህ ስንነሳ ከአፍጋኒስታን ጀምሮ ከላይ በጭፍን በሚወረወሩ ቦንቦች፣  ሰው-አልባ በሆኑ አውሮፕላን የሚሰዉ ንጹህ ዜጎች፣ ህፃናትና ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ባልቴቶች የዚህ ዐይነቱ አገሮችን የማተረማመስ ሰለባ ናቸው። ይህንን ዐይነቱን በተለያዩ አካባቢዎችና በአህጉር ደረጃ ጦርነቶችን ለማካሄድ ደግሞ ለስሙ የህግ አውጭዎች ወይም ፓርሊያሜንቴሪያን በመሰብሰብ ከህገ-መንግስቱ ጋር „አነፃፅረው“ ትክክል ነው በማለት ጦርነትን ለማካሄድ ለጄኔራሎች ፈቃድ ይሰጧቸዋል። ወታደሩንም የፓርሊያሜንት ወታደር ነው፤ እኛም የህዝብ ተወካዮች ነን፣ የምንፈጽማቸውም የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው በማለትና የውሸት ቅስቀሳ በማካሄድ የጦርነትን ህጋዊነትና አስፈላጊነት ያረጋግጣሉ። አንዳንዶች ነገሩ የሚከነክናቸው ደግሞ  ህገ-መንግስቱን ለሚጠባበቀው ፍርድቤት ክስ ሲመሰርቱ፣ ዳኞች „ክሱን ከመረመሩ“ በኋላ በፓርሊያሜንት የፀደቀው ወታደሮችን የመላኩ ጉዳይ ህገ-መንግስቱን የሚጥስ አይደለም በማለት የመጨረሻ ውሳኔያቸውን ያስተላልፋሉ።  በዚህ መልክ በረቀቀ ሁኔታ የተቆላለፉ የመንግስት መኪናዎችና ትላልቅ የካፒታሊስት ኩባንያዎች  በንጹህ ህዝብ ላይ ጦርነት እንዲካሄድ ይወስናሉ።  ይህ የሚያረጋግጠው ምንድ ነው፟? በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ለስሙ የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ እንዲሁም ህዝብን የሚወክል ፓርሊያሜንታሪ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ቢባልም፣ እንደውነቱ ከሆነ የመንግስቱ መኪናና አገዛዞች በትላልቅ ኩባንያዎች፣ በጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ፣ በወታደሩና በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው ማለት ይቻላል። የሚወጡትም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና የውጭ ፖለቲካ ከዚህ የሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ ጥቅም አንፃር እየታየ ነው። በዚህ መልክ ደግሞ በሀብታምና አነስተኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል ያለው የሀብት ክፍፍል የባሰውን እየሰፋ ሲሄድ፣ በዚያው መጠንም ሀብታሞች በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ስታተሳቸው የባሰውኑ ይጠነክራሉ። በአጭሩ በአብዛኛው የካፒታሊስት አገሮች በተለይም በአሚሪካ የኦሊጋርኪው መደብ ነው ስልጣንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠረው ።

ከዚህ ስንነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያየ ስም እየተሰጣቸው የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ የጥቂት ካፒታሊስት አገሮችን የበላይነት ለማረጋገጥ ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተለያዩ የአፍሪካ መንግስታት በዚህ ዐይነቱ የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ በመጠቃለልና በመታዘዝ በየአገሮቻቸውና በየአካባቢው ጦርነትን የሚያካሂዱ ናቸው። የእነሱ በስልጣን ላይ መቆየትና አለመቆየትም ሊወሰን የሚችለው ጦርነትን ማካሄድ እስከቻሉ ድረስና ህዝቦቻቸውን በጭንቀት ዓለም ውስጥ እስከያዙ ድረስ ብቻ ነው። አንድ ህዝብ ሲዋከብና ዕረፍት ሲያጣ ብቻ ነው ስልጣን ላይ ለመቆየት እንችላለን ብለው የሚያስቡት። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችና የተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገር አገዛዞች ሳያስቡትና ከረጅም ጊዜ አንፃር በህብረተሰብ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን በቀላሉ ሊፋቅና መፍትሄ ሊያገኝ የማይችለውን አሉታዊ ድርጊት ሳያወጡና ሳያወርዱ በከፍተኛ መሳሪያ በመታጠቅና በስለላ ድርጅት በመከበብ በህዝቦቻቸው ላይ ጦርነት ያካሂዳሉ። በዚህ መልክ ጦርነት ዓለም አቀፋዊ በመሆን የሰው ልጅ ሁሉ እንዲለምደውና የህይወቱም አንድ አካል እንዲሆንና ዝም ብሎ  እንዲመለከተው ይደረጋል። የተፈጥሮ ህግ በመሆኑም በሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ሊገታና ሊወገድ የማይችል ነገር ተደርጎ ይወሰዳል።

ስለሆነም ዛሬ በተለይም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አሸባሪዎችን ለመዋጋት ተብሎና በማዕለከኛው የምስራቅ አገሮች የሚካሄደው ጦርነት በሙሉ የካፒታሊዝም የሀብት ክምችት ዘዴ ነው። በተጨማሪም በየአገሮች ውስጥ አለመረጋጋት ሲኖር ብቻ ነው ዕድገት ሊመጣ የማይችለው። ምክንያቱም ካፒታሊዝም በመሰረቱ የሌሎችን አገሮች ጤናማ ዕድገት ስለሚቃወም ነው። ከዚህ አጭር ትንተና ስንነሳ የምዕራቡን ካፒታሊስት አገሮችንና አሜሪካንን ጨምሮ የሊበራሊዝምና፣ የዲሞክራሲ፣ እንዲሁም የነፃ ገበያና የህግ የበላይነት፣ በተጨማሪም የሰብአዊ መብት አራማጆችና ጠባቂዎች አድርጎ መመልከቱ እጅግ የዋህነት ነው፤ አላዋቂነትንም ያሳያል። በአጭሩ የሻለቃ ዳዊት ሀተታ ተቀባይነት የማይኖረውና አሳሳች የሚሆነው የላይኛውን ሀተታና ሌሎች ክሪቲካል አመለካከት ያላቸውን ጥናቶች ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሻለቃው ራሱ የዚህ ዐይነቱ በሶስተኛውም ዓለም ምስኪን ህዝቦች ላይ የሚውጠነጠነውና የሚካሄደው ጦርነት አንድ አካል በመሆኑ ነው።  የሻለቃውን ሀተታ የምንቀበል ከሆነ የጨለማውን መንገድ ተከተልን ማለት ነው። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ፀረ-የሰው ልጅ፣ ፀረ-ሰላም፣ በአገሮች መሀከል በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተን ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነትን፣ በአጭሩ ዓለም አቀፋዊ ስልጣኔን የሚቀናቀን አቀራርብና አመለካከት ነው። አሁን ደግሞ ወደ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ልምጣ።

                 

የአፍሪካ ኢኮኖሚ አድጓል ወይስ አላደገም !

ስለአፍሪካ ዕድገት ሲወራ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በየአምስት ዓመቱና በየአስር ዓመቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዚህ መጠን አድጓል እየተባለ ሲነገረን ከርሟል። ይሁንና ግን የአፍሪካ ህዝብ ኑሮ ሲሻሻል በፍጹም አይታይም። በሌላ ወገን ግን እንደዚህ እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነገር አብዛኛዎች ሰዎች፣ ራሳቸው ኤክስፐርት ነን የሚሉም የኢኮኖሚ ዕድገት ማለት ይህ ነው ብለው በመቀበልና በማስተጋባት ብዙ ሰዎችን ያሳስታሉ። ስለአፍሪካ ኢኮኖሚ በቁጥር መጨመር የሚያበስሩ ኢንስቲቱሽኖችና ኤክስፐርቶች ደግሞ በአንድ ርዕዮተ-ዓለም የሚመሩና የሰለጠኑም  በመሆናቸው ዋናው ተግባራቸው ውሸትን መንዛትና ሰውን ማሳሳት ነው። በተለይም በአፍሪካ ምድር የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ቲዎሪዎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማይሰጡበትና ክርክርም በማይደረግበት አህጉር ውስጥ ብዙ ሰዎችን፣በተለይም የፖለቲካ ኤሊቱን ማሳመን ይቀላል። እነዚህ ሰዎችም አደገ የሚባለውን ኢኮኖሚ ከካፒታሊስት ወይም ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓን፣ ከቻይናና ከተቀሩት የአሲያ ኢኮኖሚዎች ጋር ስለማያወዳድሩና ራሳቸውንም ስለማይጠይቁ፣ በየጊዜው እየተደጋገመ የሚነገረውን በአሀዝ የተደገፈውን፣ ይሁንና ግን በመሬት ላይ የሚታየውን ሁኔታ የማያንፀባርቀውን ዕድገት እየታየ ነው በማለት ተዝናንተው ይኖራሉ። ሲጠየቁ ደግሞ ከዚህ በላይ ምንድነው የምትፈልጉት፣ የኑሮ ውድነት የኢኮኖሚ ዕድገት መግለጫ ነው ወይም ነጽብራቅ ነው የማይሆንና በሳይንስ ሊረጋገጥ የማይችል ወሬ ያወራሉ።

በመሰረቱ ኢኮኖሚ ለኢኮኖሚ ተብሎ አያድግም። የኢኮኖሚ ክንውን መሰረተ-ሃሳቡ የአንድን ህብረተሰብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ነው። ማንኛውም ሰው ለመኖር ሲል የግዴታ የተለያዩ የምግብ ዐይነቶች፣ ንጹህ ውሃ፣ መጠለያ፣ ማሞቂያና መቀቀያ፣ ህክምናና መሰረታዊ ትምህርት ማግኘት አለበት።  እነዚህ የኢኮኖሚ መሰረተ ሃሳቦች ናቸው። ከዚህ ወጣ ብለን የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ ይህንን በቁጥር እያደገ የሚሄድ ህዝብ ለማስተናገድ ኢኮኖሚው በስርዓት መዘጋጀት ወይም መታቀድ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ቴክኖሎጂና ሳይንስ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በሌላ አነጋገር በሳይንስ ምርምር ላይ የተመረኮዘ የቴክኖሎጂ ምጥቀት በማይታይበትና በዚህም አማካይነት ምርታማነትን ለማሳደግ በማይቻልበት አገር ውስጥ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም መናገር አይቻልም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከዘመናዊ ኢንስቲቱሽን መስፋፋትና ከዕውቀት ጋር የሚያያዝ ነው። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ ያለ የተመጠነ የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል በኢንስቲቱሽኖችና በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው ሊንቀሳቀሱና በምርት ክንዋኔ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉት። ከዚህም በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በቦታና በጊዜ የሚወሰን ነው። ይህም ማለት የከተማዎችና የመንደሮች ጥበባዊ በሆነ መልክ መታቀድና መገንባት፣ እንደዚሁም እነዚህ ደግሞ በተለያየ የመመላለሻ ነገሮች መተሳሰርና፣ ዕቃዎች፣ ካፒታልና የሰው ኃይል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በተቀላጠፈ መልክ መመላለስ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕና አላቸው። እነዚህ ነገሮችና፣ በተጨማሪም በቴክኖሎጂ ላይ ተደግፎ የሚንቀሳቀስ የማዕከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ በሌለበትና ውድድር በማይካሄድበት አገር ውስጥ ስለኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም ማውራት አይቻልም።

ባለፉት አስር ዓመታት በአፍሪካ ምድር አድጓል እየተባለ የሚለፈፈውን ኢኮኖሚ በምንመረምርበት ጊዜ፣ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ጭምር የአገልግሎትና የንግድ መስኩ ነው እየተስፋፋ የመጣው። የሚሰሩትም ሆቴል ቤቶችና ትላልቅ ህንጻዎች ደግሞ የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጐቶች የሚያሟሉ ሳይሆኑ ለጥቂቱ ኢሊትና ከውጭ በኤክስፐርት ስም ለሚመጡ የሚያገለግሉ ናቸው። ይህ ዐይነቱ የአገልግሎት መስክ መስፋፋት ደግሞ በየአገሮች ውስጥ ያለውን የጥሬ-ሀብትና ገንዝብ፣ እንዲሁም ኃይል(Energy) የሚጋራ በመሆኑ ለኑሮ ውድነት ዋነኛውም ምክንያት ነው። ትላልቅ ሆቴል ቤቶችና ህንጻዎች በከፍተኛ ደረጃ ኃይልና ውሃ ስለሚጋሩ በተለይም እንደ አዲስ አበባ፣ ሌጎስና ናይሮቢ የመሳሰሉ ከተማዎች ሰፊውን ህዝብ እያሰቃዩ ነው። በዚህ መልክ የሚካሄደው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የባሰውኑ የአገር ውስጥ ሀብት ወደ ውጭ እንዲወጣ የሚያደርግና የንግድ ሚዛኑንም የሚያናጋ ነው። ያም ሆኖ አድጓል እየተባለ የሚለፈፈውን ኢኮኖሚ ጠጋ ብለን በምንመረምርበት ጊዚ ብዙ ዕቃዎች፣ ለህንጻና ለመለዋወጫ እንዲሁም በግማሽ የተፈበረኩ ዕቃዎች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው እነዚህ ለኢኮኖሚው ዕድገት ዕምርታን ይሰጡታል።  በአንድ አገር ውስጥ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚወራው ላይ ከዘረዘርኩት ባሻገር ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎችና የምርት ክንውን ውስጥ የሚገቡ የመጨረሻ መጨረሻ ከስሌቱ ከወጡና የአገር ምርት ክንውን በንጹህ መልክ ከተሰላ ስለ ኢኮኖሚው ማደግና አለማደግ አንዳች ስዕል ማግኘት ይቻላል።

ያም ተባለ ይህ  ኢኮኖሚው በፍጥነት አደገባቸው በሚባሉ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም አንጎላና ኢትዮጵያ፣ እነዚህ አገሮች አሁንም ቢሆን በውጭ ኤክስፖርታቸው በአንድና በሁለት የጥሬ ሀብቶች ብቻ  የሚመኩ ናቸው። አንጎላ ከሰማንያ በመቶ በላይ በሚሆነው ገቢዋ በዘይት ስትመካ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በቡና፣ በሰሊጥ በቆዳና በአበባ እንዲሁም በጨአት የምትመካ ነች። ይህም የሚያረጋግጠው እነዚህ አገሮች  እንደሚነገረው ይህንም ያህል በኢኮኖሚ ዕድገታቸው እንዳልገፉ ነው። የውስጥም ያለው ሁኔታ(Social and Economic structure) እንዳልተለወጠ በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮች ያረጋግጣሉ። በግሎባላይዜሽንና በነፃ ንግድ የተነሳ እንዲያውም የሁለቱ አግሮች ኢኮኖሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በጠቅላላው ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገር ኢኮኖሚዎች በሙሉ የባሰ የተቅዋም ቀውስ(Structural crisis)ይገኛሉ።  ከዚህ ስንነሳ በምድር ላይ የሚታየው ሃቅ የሚያስገርም አይደለም። በከተማዎች ውስጥ የቆሻሻ መኖሪያዎች መስፋፋት፣ ከተማዎች ከውጭ የሚመጡ የሰከንድ-ሃንድ ዕቃዎች መጣያ መሆን፣ ወጣቱ ስራና የሙያ ማሰልጠኛ ቦታ አጥቶ መንቀዋለል፣ በገጠርና በከተማ መሀከል ያለው ልዩነት መስፋፋት፣ የባህል ዝቀትና የሴተኛ አዳሪዎችና የሸፍጠኞች መብዛት፣…  ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንዳለደገ ነው። ብዙ ማውራት ቢቻልም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች አሁንም ባላቸው መንግስታዊ አወቃቀርና፣ በዚህም አማካይነት በኤሊቱና በውጭው ኃይል በሚካሄድ የሀብት ዘረፋ የተነሳ ኢኮኖሚያቸው ወደ ገበያና ብሎም ወደ ካፒታሊስት የምርት ክንውን ሊሸጋገር አይችልም። በአፍሪካ አገሮች ውስጥ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የግዴታ እያንዳንዱ አገር ከውጭ ተጽዕኖ መላቀቅና በሳይንስ ላይ የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ አለበት። ጠቅላላውን በየአገሮች ውስጥ የሚታየውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የህሊና ቀውስ፣ የአካባቢ ቀውስና የመሰረታዊ ፍላጎቶችንም ችግሮች ለመፍታት ወደድንም ጠላንም እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ሁለንታዊ የሆነ(Holsitic Model) የኢኮኖሚ ዕቅድ ማካሄድ ወይም ተግባራዊ ማድረግ አለበት። የአገራችንንም ሆነ የተቀሩትን የአፍሪካ አገሮች ችግሮች በፕሮጀክት ደረጃ ወይም በነጥብ በነጥብ እየወሰድን የምንፈታው ሳይሆን፣ ክላሲካል የሆነ የችግር አፈታት ዘዴን የተከተልን እንደሆን ብቻ ነው።  ለዚህ ደግሞ የመንግስታት አወቃቀር መለወጥና ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ ባህርያ ያላቸው ኢንስቲቱሽኖች መቋቋምና መዳበር አለባቸው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በራሱ የሚተማመን፣ ከውጭው ዓለም ጋር ያልተሳሰረ ሁለንታዊ ዕውቀት ያለው አገር ወዳድ የፓለቲካ ኤሊትና ምሁራዊ ኃይል ያስፈልጋል። ንቃተ-ህሊናው ከፍ ያለ፣ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ራሱ በችግር ውስጥ ያለፈና ችግር ማለት ምን እንደሆነ የገባውና ከህዝቡ ጋር ሆኖ በጋር ችግሩን ሊቀርፍ የሚችል ስነ-ምግባር ያለው ኤሊት መኖር አለበት። ይህ ዐይነቱ የኤሊት ኃይል በሌለበት አገር ስለኢኮኖሚ ማደግና ስለ ብሄራዊ-ነፃነት፣ ስለዲሞክራሲና ስለ ሰብአዊ መብት መከበር  በፍጹም ማውራት አይቻለም።

ከዚህ አጠር ያለ ሀተታ ስነሳ ሻለቃ ዳዊት ያላያቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ። እሱ በአሃዝ መልክ ብቻ ባስቀመጠው ስለአንድ አገር ኢኮኖሚ አለማደግ ማተት አይቻልም። ከላይ ባስቀመጥኩት መሰረት በአንድ አገር ውስጥ ኢኮኖሚ ዕድገት አለ የሚባለው በዚያ አገር ውስጥ ብሄራዊ ሀብት ሲዳብርና፣ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ሲገነባ ብቻ ነው። ለዚህ መሰረቱ ደግሞ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ማኑፋክቱርና ሰፋ ያለ የስራ -ክፍፍል መዳበር ናቸው። በዚህ መልክ የማይተነተንና የማይቀርብ የኢኮኖሚ ሀተታ ብዙ ሰውን ያሳስታል።

    መደምደሚያ !

ከላይኛው አጠቃላይ ሀተታ ስንነሳ ለዲሞክራሲያዊና ለሰብአዊ  መብት፣ ለነፃነትና ለሰላም እንታገላለን የምንል ኃይሎች በሙሉ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱትንና፣ ለብዙ መቶ ሺህ ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑትን ጦርነቶች ዋና መነሻ ማጥናትና መመርመር ያስፈልጋል። በየጦር ሜዳው ላይ ህይወታቸውን የሚሰዉት ምስኪን ህዝቦችና ትዕዛዝ እየተቀበለ በንጹህ ህዝብ ላይ እንዲተኩስ የሚደረገው ተራ ወታደር ነው። ጂኔራሎች ትላልቅ መኮንኖችና ፖለቲከኛ ነን ባዮች የጦር ሰለባ ሆነው አያውቁም። የሚሆን የማይሆን ምክንያት እየፈጠሩ ህዝብን ሲያጫርሱ እነሱ ተንደላቀው ይኖራሉ። ለምሳሌ የአንድ ኦኬስትራ አቀነባባሪ(Conductor)ተግባርን በምንመለከትበት ጊዜ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወቱ ሙዚቀኞችንና ድምጻውያንን ከፈለገና ረጅም ጊዜ ካለማመደ በኋላ አዳማጩን ወይም ተመልካቹን ሊያስደስት የሚችል ኦኬስትራ ያሰማል። ዓላማውም ለማስደሰት ብቻ ሳይሆን በዚያው መጠንም በተመልካቹ ወይም በአድማጩ ልብ ውስጥ የሙዚቃን ፍቅር ለማሳደርና ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው። አንድ ጥሩ ልበ-ወለድ ጸሀፊም ተጨንቆ፣ ተጠቦና ተፈላስፎ ከረጅም አመታት በኋላ አንድ የተዋጠለት ልበ-ወለድ ለአንባቢው ሲያቀርብ የሚያስተላልፈው  ትምህርታዊ ነገር አለ። እንደሰውየው ዝንባሌ ልበ-ወለዱ ህብረተሰብአዊ ትችትን ያዘለ ወይም ተፈጥሮን የሚቃኝ ወይም ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሶ ያለፈበትን ህይወት ትዝታን የሚመለከት ይሆናል። የሌሎችም፣ የዘፋኞች፣  የስፖርተኞች፣ የቀልድ አቅራቢዎችና ካባሬቲስቶች ሙያ በሙሉ በአጠቃላይ ሲታይ መልዕክቱ ሰውን ከማሳቅና ከማስደሰት ባሻገር የሰውን ባህርይ ለመግራትና ሰው መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ባጭሩ የሰው ልጅ ተግባር ጦርነትን ማካሄድ ሳይሆን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን፣ እንዲሁም መተባበርን  ለማስተማርና ለማስታወስ ነው።

ወደ ፖለቲከኞች፣ ኢኮኖሚስት ነን ባዮችና ወደ ሚሊታሪ ሰዎች ስንመጣ ግን ስራቸው በሙሉ የሰውን ህይወት ማክበድ ነው። ቀላል ነገሮችን እያወሳሰቡ የሰው ልጅ በጭንቀት ዓለም ውስጥ እንዲኖር እያደረጉ የሚሄዱ ናቸው። በተለይም ከካፒታሊዝም ሎጂክ ጋርና ከበላይነት መንፈስ ጋር የተቆራኙ የሚሊታሪ ሰዎች ተግባራቸው በሙሉ እንዴት አድርገን ጦርነት እንቀስቅስ፣ እንዴት አድርገን ዓለምአቀፋዊ ባህርይ እንስጠው የሚል ነው። የኞ ተግባርም ይህን ዐይነቱን ስላም የሚነሳን፣ ኃይልን የሚጨርስን፣ በህዝቦች መሀከል አለመግባባትን የሚፈጥረውን፣ በሃይማኖትና በጎሳ ስም ተሳቦ በየአገሮች የሚካሄደውን ጦርነት መነሻ ዋና ምክንያት እያጠኑና፣ አወጠንጣኖችን እያጋለጡ በአንድ አገር ውስጥ ስላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው እያንዳንዱ ዜጋ የመንፈስ ነፃነት በማግኘት ፈጣሪና ምርታማ ሊሆን የሚችለው።፡ስለሆነም ዋናው ሚናችንና ዓላማችን በምንም ዐይነት የሰላዮችና የጦር ስልት አውጭዎች ሰለባ መሆን አይደለም። መንፈሳችንን በማጠንከርና በራስ በመተማመን ካልተማረው ህዝብ ጎን በመቆም እፎይ ብሎ የሚኖርበትን ሁኔታ የመፍጠር ሞራላዊ፣ ህብረተሰብአዊና ታሪካዊ ግዴታ አለብን። መልካም ግንዛቤ !! 

                                                             ፈቃዱ በቀለ

                                                 fekadubekele@gmx.de