[gtranslate]

የሐገርን ኢኮኖሚ እየገደለ ያለው አዲሱ የብሄራዊ ባንክ ገዢ በሚል አርዕስት ስር በአቶ ሳሙኤል ብዙነህ የቀረበውን አጭር ጽሁፍ በሚመለከት የተሰጠ የድጋፍ ሀተታና፣

የአቶ ጌታቸውን መሰረተ-ቢስ ትችት የሚቃረን ገለጻ!

                                                             ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                             ጥር 31፣ 2023

ውድ ወንድማችን አቶ ሳሙኤል ብዙነህ “የሀገርን ኢኮኖሚ እየገደለ ያለው አዲሱ የብሄራዊ ባንክ ገዢ” በማለት ያቀረበውን  ጽሁፍ አቶ ጌታቸው  እንደ ጽንፈኛ አቀራረብ አድርጎ ነው የቆጠረው። ጽንፈኛ የሚባለው ዘላፊ ጽንሰ-ሃሳብ ከኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር ምን እንደሚያያይዘው ሊገባኝ በፍጹም አይችልም።

ወደ ቁም ነገሩ እንምጣና ውድ ወንድሜ አቶ ጌታቸው የቱን ያህል ስለኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ዕውቀት እንዳለህ ለማወቅ ባልችልም፣ ከአጻጻፍህ ለመገንዘብ እንደቻልኩት ከሆነ በአገራችን ምድር በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በደንብ የተከታተልክ አለመሆንህን ነው። በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ ፖሊሲ ሳይሆን አገዛዙን ዘራፊ በማድረግ፣ የውጭና የውስጥ ግብረአበሮቹን እንዲጠቅም ሆኖ የተመቻቸ  በኢኮኖሚ ፖሊሲ ስም አብዛኛውን ህዝባችንን ወደ ድህነት የገፈተረ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆነ የአገራችንን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ያዘበራረቀና ለብዙ ዓመታት ዐይነተኛ መፍትሄ እንዳይገኝለት መሰረት የጣለ ኢ-ሳይንሳዊና ፀረ-ህዝብ ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል።  ምክንያቱም የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ ሳይንሳዊ መሰረት ካለው አንድን ህዝብ ከድህነት ያወጣዋል፤  አንድን አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ያደርጋል፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤትም በማድረግ ኢኮኖሚው በቴክኖሎጂ ላይ እንዲመሰረት ያደርገዋል። በዚህም አማካይነት የተከበረና በቀላሉ የማይደፈር አገር መገንባት ይቻላል። ሃይንሪሽ ፔሽ በሚባለው ታላቅ የጀርመን ኢኮኖሚስት አስተሳሰብ መሰረት የኢኮኖሚ ዋናው ተቀዳሚ ተግባር የሰውን ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) ማሟላት ነው ይላል። ሌሎች የተገለጸላቸው የኢኮኖሚና የፍልስፍና ምሁራን ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ። ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው የ19ኛው ክፍለ-ዘመን ታላቅ ኢኮኖሚስትና የፍልስፍና ምሁር የእነ አዳም ስሚዝን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመቃወም አንድ አገር ኢኮኖሚዋን ለውጭ ንግድ ልቅ ከማድረጓ በፊት የግዴታ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ መገንባት አለባት ይላል። በእሱ ዕምነት በጥሬ-ህብትና በእርሻ ላይ ብቻ የምትመካ  አገር በባህልም ሆነ በልዩ ልዩ ጥበባዊ ነገሮች ልታድግ አትችልም። ለህዝብ ልዩ ልዩ ግልጋለቶችን የሚሰጡ የሰለጠኑ ተቋማትንም ለመገንባት አትችልም።  በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች(Infant Industries)ከውጭ በሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች ስለሚጠቁ የማደግ ኃይላቸው በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ከውጭ የሚመጣው ዕቃ ዋጋው ርካሽ ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ ይችላሉ። ስለሆነም ህዝቧም ከውጭ በመጡ ወራሪዎች ይጠቃል ይለናል፤ ሰው መሆኑንም ይዘነጋል ይላል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ህዝብና አገር ብሄራዊ ነፃነታቸውን ለማስከበርና ወደ ውስጥ ደግሞ የተረጋጋ አገር ለመገንባት ከፈለጉ ኢኮኖሚያቸውን በማኑፋክቸሪንግ ላይ መሰረት በማድረግ መገንባት አለባቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የግዴታ ተከታታይ ዕድገት እንዲመጣ ከተፈለገ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ኃይል መሆን አለባቸው። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው የሰውም አስተሳሰብ የሚሻሻለውና አጭበርባሪ የማይሆነው። ምክንያቱም አንድ ህዝብ ኢንደስትሪየስ ከሆነ የበለጠ በፈጠራ ስራ ላይ ስለሚያተኩር የማጭበርበርና ተንኮል የመስራት ፍላጎቱ በከፍተኛ ኃይል ይቀንሳል። ስራው ሁሉ አርቆ አሳቢነት በመሆን ሁሉንም ነገር በስነስርዓትና ህዝብን በማይጎዳ መልክ ይሰራል።  ይህንን መሰረት በማድረግ ነው አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚያቸውንና አገራቸውን መገንባት የቻሉት።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት ሲወጣ በነፃ ገበያ ስም አሳቦ በተለይም እንደኛ የመሰሉ አገሮች ወደ ውስጥ ያተኮረና ህዝቡን የሚያስተሳስር ኢኮኖሚ እንዳይገነቡ አገደ። በተለይም እነሳሙኤልሰን ያስፋፉት የተሳሳተ የኢኮኖሚክስ መማሪያ መጽሀፍ በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የመማሪያ መጽሀፍ በመሆኑ ኢኮኖሚክስን ተምረው የሚመረቁ ኢኮኖሚስት ነን ባዮች የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ከታች ወደ ላይ እንዴት እንደተገነባ እንዳያውቁ ተደረጉ። በተለይም ነፃ ገበያ የሚለው አስተሳሰብ በመስፋፋቱ የአንድን አገር ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ሳይኖር ብቻ ነው የሚለው ተቀባይነት በማግኘቱ የአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም መንግስታት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ታገዱ። ምክንያቱም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት እንደ ሀጢአት ወንጀል  በመቆጠሩ። ወደ ካፒታሊስት አገሮች ስንመጣ ግን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የየመንግስታቱ ጣልቃ-ገብነት ከፍተኛ እንደነበረ ብዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።  የነፃ ገበያና ንግድ አስተሳሰብ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ከማለቱ በፊት የፍጹም ሞናርኪዎች በመባል የሚታወቁት የአገራቸውን የውስጥ ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ይታወቃል። ከተማዎች፣ መንደሮችና የካናል ሲይስተሞች የተገነቡት በነገስታት ከፍተኛ ርብርቦሽ ነው። ከዚህም በላይ በኢኮኖሚ ግንባታ ልዩ ተሰጥዖ የነበራቸው በተለያዩ ዘዴዎች በመንግስታት ይደጎሙ ነበር። በየአገሮች ውስጥ የሚመረተው ምርት ከውጭ በሚመጣው ተመሳሳይ ምርት እንዳይጠቃ ልዩ ዐይነት የዕገዳ ፖሊሲ ይካሄድ ነበር። ስለሆነም ይህንን ፖሊሲ መስረት በማድረግ ነው አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ለካፒታሊዝም ኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል የቻሉት። ይህ መሰረት ነው የኋላ ኋላ አዳምስሚዝ የረቀቀው እጅ(Invisible Hand) ለሚለው የየግለሰቦች ተሳትፎ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር የቻለው። በኋላም  በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተነሳ ኢኮኖሚያቸው የተንኮታኮተው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ሊያንሰራሩ የቻሉት በከፍተኛ ደረጃ በመንግስታት ጣልቃ- ገብነት ብቻ ነው። በተለይም ኬይንስ የሚባለው የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶችን ምክርና መመሪያ የሚተቸው ካለመንግስት ጣልቃ-ገብነት በተለይም እንደካፒታሊስት አገሮች የመሳሰሉት ኢኮኖሚዎች ተከታታይነት ያለው ዕድገት ሊያሳዩ አይችሉም ይላል። ኬይንስ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊትና፣ በተለይም በ1929 ዓ.ም የደረሰውን ትልቁን የኢኮኖሚ ቀውስና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰራተኞች ከስራ ቦታቸው ለመባረራቸው ምክንያት የሆነውን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሰፊውና በጥልቀት ካጠና በኋላ ኢኮኖሚው ከቀውሱ እንዲላቀቅ ከተፈለገ መንግስታት ከባንክ በመበደርና ኢንቬስት በማድረግ ኢኮኖሚው እንዲያገግም ማድረግ አለባቸው ይላል። በእሱ ዕምነትም በተለይም በአንድ አገር ውስጥ ማህበራዊ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ መንግስት በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት ጣልቃ በመግባት የስራ መስክ ሊከፈት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት ይላል። መንግስት እንደዚህ በማድረጉ በምንም ዐይነት የየግለሰቦችን ተሳትፎ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊቀንሰው አይችልም። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ምርቶች በግል ካፒታሊስቶች ስለሚመረቱ ከመንግስት ኮንትራት ካገኙ የግዴታ እንዲያመርቱ ይገደዳሉ። በዚህም አማካይነት በቂ የስራ መስክና በቂ የሆነ የመግዛት ኃይል እንዲፈጠር ለማድረግ ይችላሉ ይላል።

አባዛኛዎቹም የካፒታሊስት አገሮች ይህንን የኬይንስን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክር በመቀበል ነው ከሞላ ጎደል ሚዛናዊነት ያለው ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ ለመገንባት የቻሉት። በተለይም እንደጀርመን የመሳሰሉት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተነሳ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳባቸው፣ ቤቶች የፈራረሰባቸው፣ ከተማዎች የወደሙባቸውና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በድህነትና በረሃብ የተሰቃየባቸው አገሮች  ተግባራዊ ያደረጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኬይንስ ካለው የበለጠ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ነው በ15 ዓመት ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረ ኢኮኖሚ በመገንባት፣ ወደ ውጭ ደግሞ ከአሜሪካን ጋር መወዳደር የቻሉት። ከላይ እንዳልኩትም የኢኮኖሚው ዋና መሰረት ማኑፋክቸሪንግ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በተከታታይ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምርምርና ውጤት የተደገፈ  በመሆኑ ኢኮኖሚው በቀላሉ ሊያድግና ሊስፋፋ ቻለ።  በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ በተሟላ ሁኔታ ከተማዎች ማበብና የንግድ እንቅስቃሴዎች መስፋፋት ቻሉ። በየቦታውም የመመላለሻ መንገዶችና የባቡር ሃዲዶች በመስፋፋታቸው የዕቃ፣ የሰውና የካፒታል ዝውውር ለመዳበርና ለመፋጠን ቻለ። በዚህም አማካይነት የተነሳ የውስጥ ገንዘቡ ከልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎችና የንግድ እንቅስቃሴዎች ጋር በመያያዙና በፍጥነትም በመሽከርከሩ፣ በአንድ በኩል ካፒታሊስቶች እንደገና ለመዋዕለ-ነዋይ የሚሆን ካፒታል ሲያገኙ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የገንዘቡ የመግዛት ኃይል ከፍ ሊል ቻለ።  ጠቅላላው ኢኮኖሚውን ለመገንባት ደግሞ እንደጀርመን የመሳሰሉት መንግስታት ከሁለተኛው ጦርነት ማለቂያ በኋላ በማርሻል ፕላን የተደገፈ ዕርዳታ ቢያገኙም የራሳቸውን ልዩ የክሬዲት ሲስተም በመመስረት ነው በተለይም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በቅናሽ ክሬዲት መደገፍ የጀመሩት። ይህም ማለት፣ በጀርመን አገርም ሆነ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በተለይም ከ1950-1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም በህዝቡና በባንኮች መሀከል ከፍተኛ ትስስር ነበር።  ምክንያቱም ኢንዱስትሪዎች ኢንቬስት ለማድረግ ሲፈልጉ ከባንኮች ስለሚበደሩና  መልሰውም ወለድ ስለሚከፍሉ ነው። በደሞዝ የሚተዳደሩት ደግሞ የተወሰነውን ለቤት ኪራይና ለልዩ ልዩ ዕቃዎች ካዋሉ በኋላ የተወሰነውን ባንኮች ውስጥ ስለሚያስቀምጡ ባንኮች የሚያበድሩትን ገንዘብ ያገኛሉ ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ቤት ለመስራትና መኪና ለመግዛት ደሞዛቸው የማይበቃቸው ሰራተኞች  ከባንኮች ገንዘብ ስለሚበደሩ በዚህም ምክንያት የተነሳ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሽከረከረው ገንዘብ የመግዛት ኃይሉም ከፍ ለማለት ቻለ።

ወደ ኢትዮጵያና የተቀሩት የሶስተኛ ዓለም አገሮች ስንመጣ ግን በየአገሮች ውስጥ የበሰለ መንግስትና ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ እነዚህ አገሮች ለውጭ ኤክስፐርቶች እንዲጋለጡ ለመደረግ በቁ። በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚ ቲዎሪና ሳይንስ ስለማይታወቁ፣ ክርክርም ስለማይካሄድና፣ ከዚህም በላይ ደግሞ የካፒታሊስት አገሮችና እንደጃፓን የመሳሰሉ እንዴት ለማደግ ቻሉ ተብሎ ክርክርና ጥናት ስለማይደረግ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተግባራዊ የሚያደርጉት ፖሊሲ የነፃ ገበያ የሚባለውንና፣ እንደ ዓለም´ የገንዘብ ድርጅትና እንደ ዓለም ባንክ በመሳሰሉት የሚሰበከውን “ቅዱሳዊ አስተሳሰብ” የሚመስሉትን “ፖሊሲ” ብቻ ሆነ። ስለሆነም ሁሉም ነገር ወደ ገበያ ተቀንሶ መታየት በመቻሉ ከኢንዱስትሪና ከማኑፋክቸሪንግ ይልቅ የአገልግሎት መስኩ፣ በተለይም የንግድ መስኩ መንዛዛት ቻለ። እንደሚታወቀው በኢኮኖሚክስ ህግ መሰረት ከንግድ በፊት የሚቀድመው ምርት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የንግድ እንቅስቃሴ ሊዳብር የሚችለው አንድ አገር የማምረት ኃይሏ ከፍ ሲል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን የማምረት ኃይል በሁሉም ዘርፍ በተስተካከለ መልክ መዳበር አለበት። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ አስተሳሰብ ይህንን መሰረታዊ የሆነ የኢኮኖሚ ህግና አስተሳሰብ በመቃወም በምሁር አስተሳሰብ በደንብ ያልበሰሉ እንደኛ የመሳሰሉትን አገዛዞች በመምከር መቀመቅ ውስጥ ይከቷቸዋል። በእኛና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ጣልቃ-ገብነትና ምክር ከስድሳ ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም እኛም ሆን የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ከድህነትና ከረሃብ አልተላቀቅንም። ያውም የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት እያለንም።  ሌላው ኢ-ሳይንሳዊ የሆነው የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስለህዝብና ስለ ህብረተሰብ ምንም ነገር አያወሩም።  እንደሚታወቀው ኢኮኖሚ ማደግና መስፋፋት ያለበት ለገበያ ተብሎ ሳይሆን ለሰው ልጅና ህብረተሰብ ብቻ ነው። ህዝብንና አገርን ማዕከል ያላደረገ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ደግሞ ድህነትንና መዝረክረክን ነው የሚፈጥረው።  ከዚህም በላይ እነዓለም የገንዘብ ድርጅት የመሳሰሉት፣ በአጭር አባባል የዓለም ኮሙኒቲው በመባል የሚታወቁት ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው መሰረት ማኑፋክቸሪንግ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሆን እንዳለባቸው አያስተምሩም። በፖሊሲያቸውም ውስጥ አያካትቱም።

ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ(IMF & World Bank)ከፍተኛውን ሚና መጫወት ከጀመሩ ከ1980 መጀመሪያ አንስቶ በየአገሩ ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ በተለይም የአፍሪካ መንግስታት የተቅዋም መስተካከያ ዕቅድ(Strucctural Adjustment Program) ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስገደድ ጀመሩ። ቀደም ብሎ ግን በአፍሪካውያን ኢኮኖሚስቶችና ምሁራን የሌጎስ ፎር አክሽን (Lagos for action) የሚል ኡለ-ገብና ፍቱን ፖሊሲ ረቆ ለአፍሪካ መንግስታት ይቀርባል። እነሱም በዚህ በመስማማት ተግባራዊ ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ ሳሉ ይህንን የሰሙት የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የመሳሳሉት በአማሬካን መንግስት በመላክ ዕቅዳቸው እንዲጨናገፍ ይደረጋል። በእነሱ አስተሳሰብ መሰረትም ከእነሱ ፈቃድ ውጭ አንድ የአፍሪካ አገር የራሱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማውጣት የለበትም። ስለሆነም በዓለም የገንዘብ ድርጅና በዓለም ባንክ የረቀቀውን ፕሮግራም ብቻ ተግባራዊ ሲያደርጉ ነው ብድር የሚያገኙት። በሌላ ወገን ደግሞ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በምንም ዐይነት ብድር አያስፈልጋቸውም። ምክንያቱም ከጥሬ-ሀብትና ከዘይት ሺያጭ የሚገኘው ዶላር ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው በበቃ ነበር። ይሁንና አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታት ከጥሬ-ሀብት ሺያጭ የሚያገኙትን ዶላር ለቅንጦት ዕቃዎች ስለሚያወጡና፣ የተወሰነውም የውጭ ምንዛሪ ስለሚሸሽ ወይም በዚያው በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ስለሚቀር በዚህ ምክንያት የተነሳ ኢኮኖሚያቸውን ፋይናንስ ለማድርግ በቂ ዶላር ማግኘት አይችሉም። ስለሆነም ከፋይናንስ ገበያና ከዓለም የገነዝብ ድርጅት በመበደር የወለድ ወለድ(Compound Interest) እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። በዚህና በተከተሉት ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ለህዝቦቻቸው አስተማማኝ የሆነ የውስጥ ገበያና ኢኮኖሚ መሰረት መገንባት በፍጹም አልቻሉም።

የዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢ-ሳይንሳዊ የሚያሰኘው የእነሱ ዕቅድ በአንደኛውም የኢኮኖሚ መጽሀፍ ውስጥ እንኳ ተጽፎ አይገኘም። በዩኒቨርሲቲ ውስጥም በዚህ መልክ ተስጥቶም አያውቅም። አብዛኛዎቹ ተማሪዎችም ሰለኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ስለማይማሩ፣ ከተመረቁና የመንግስት መስሪያቤት ውስጥ ሲቀጠሩ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ያወጡትን ፖሊሲ ብቻ ተግባራዊ  እንዲያደርጉ ይገደዳሉ። በዋሽንግተን ስምምነት ላይ ተረቆ በቀረበው ፖሊሲ መሰረት፣ 1ኛ) የአብዛኛዎች የአፍሪካ አገር ከረንሲዎች ከዶላር ጋር ሲነፃፀር መቀነስ(Devalue) አለበት። በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዕምነት ገንዘባቸው ከሚገባው በላይ ስለተተመነ(Overvalued) በዚህም ምክንያት የተነሳ ወደ ውጭ የሚልኩትን የጥሬ-ሀብት እንደልብ ለመሸጥ አይችሉም። ገንዘባቸውን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ከቀነሱ ግን ይበልጥ መሸጥ ይችላሉ፤ ስለሆነም በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ ያገኛሉ ይላሉ። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ኢላስቲሲቲ ኦፍ ዴማንድ(Elasticity of Demand) በመባል ሲታወቅ፣ አንድ አገር የገንዘቧን ትመና በአንድ ፐርሰንት ብትቀንስ የምትሸጠውም የምርት መጠን እንደዚሁ በአንድ ፐርሰንት ያድጋል ይላል።  ይሁንና ግን ስታትስቲክሶች እንደሚያሳዩትና እንደሚያረጋግጡት ከሆነ ከረንሲያቸውን የቀነሱ አገሮች በሙሉ የንግድ ሚዛናቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደተዛባ ነው። ለምሳሌ  ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው 70% ቡና ሲሆን፣ ከዚህና ከሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በ 2021 ዓ.ም 3.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብቻ ስታገኝ፣ ከውጭ ላስመጣቻቸው ልዩ ልዩ ዕቃዎች ደግሞ  ክ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገች ስታትስቲክሱ ያሳያል። ይህም ማለት፣ የውጭ ንግድ ሚዟና በከፍተኛ ደረጃ የተዛባ ሲሆን፣ ይህም ወደ 11,7 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። ወደ ውጭ ከላከችው ወደ ውስጥ ያስገባችው በጣም ከፍ ያለ ነው ማለት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ዕዳዋም በከፍተኛ ደረጃ ተቆልሏል። ከቻይናና ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ የተበደረችው ጠቅላላ ዕዳ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ሲጠጋ፣ ከቻይና ብቻ 12 ቢሊዮን ዶላር ተበድራለች። ይህም ማለት አገራችን ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠችና፣ መንግስት ወይም አገዛዙ ኢኮኖሚውን በፈለገው መልክ ለማደራጀትና ለሰፊው ህዝብ ደግሞ  በቂውን ግልጋሎትና ለሰው ህይወት ጠቃሚ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ በፍጹም አይችልም ማለት ነው።

ይህም የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ ዝቅ ማድረጉ ጤናማ ኢኮኖሚ እንደንገነባና ነፃ እንድንሆን አላዳረገንም።  ከዚህም በላይ እንደቡና የመሳሰሉትን ምርቶች ሌሎች አገሮችም ስለሚያመርቱና በኮታም ስለሚሸጥ አንድ አገር ገንዘቧን በመቀነሷ የግዴታ በብዙ ሚሊዮን ቶን የሚቆጠር ቡና ልትሸጥ አትችልም። ይህ ዐይነቱ የገንዝብ ቅነሳ ሊሰራ የሚችለው በቴክኖሎጂ ላደጉ አገሮች ብቻ ሲሆን፣ እነዚህም አገሮች በመንግስት ወይም በባንክ ጣልቃ-ገብነት ገንዘባቸውን መቀነስ አያስፈልጋቸውም። በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ባለው ውድድርና በተለያዩ የፖለቲካና የጦርነት ምክንያቶች የተነሳ፣ ለምሳሌ ካፒታል ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ በሚሸሽበት ጊዜ የዶላር ትማኔ ከኦይሮ ጋር ሲነፃፀር ከፍ ሊል ይችላል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ አውቶማቲክ ዲቫሉዌሽን(Automatic Devaluation) በመባል ሲታወቅ፣ ኦይሮ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በሚቀንስበት ጊዜ እንደ ጀርመን የመሳሰሉት ለኢንዱስትሪ ተከላ የሚያገለግሉ ማሺኖችንና ልዩ ልዩ የመለዋወጫ ዕቃዎችን የሚያመርቱ አገሮች ምርቶቻቸውን በብዛት ለመሸጥ ይችላሉ። ምክንያቱም አንድ የውጭ አገር ኩባንያ ወይም አገር አንድ ኦይሮ ለመግዛት ከፈለገ አንድ ኦይሮን ከአንድ ዶላር በታች ስለሚገዛ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ እንደጀርመን የመሳሰሉት ኢኮኖሚዎች ማሺኖችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን በብዛት ስለሚሸጡ በውጭ ንግዳቸው ጤናማ ይሆናሉ ማለት ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ ህወሃት ስልጣን ከያዘ በኋላ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን(IMF) ምክር በመቀበሉና የኢትጵያንም ብር በተከታታይ እንዲቀንስ በማድረጉ የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ መዛባቱ ብቻ ሳይሆን፣ በዕዳም እንድትተበተብ ለመሆን በቅታለች። ከዚህ በተረፈ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ እንዲቀንስ መደረጉ ወደ ውስጥ የመግዛት ኃይሉንም በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንዲል አድርጎታል። በተለይም ከወጭ የመለዋወጫ ዕቃዎችንና ማሽኖችን የሚያስመጡ አምራቾች የኢትዮጵያ ብር ዝቅ በሚልበት ጊዜ አንድ ዶላር ለመግዛት ከድሮው ጋር ሲወዳደር ብዙ የኢትዮጵያ ብር መክፈል አለባቸው ማለት ነው። ይህ በራሱ ደግሞ የማምረቻ ዋጋን ከፍ ያደርገዋል። ይህም ማለት ምርቱ በገበያ ላይ ይወደዳል ማለት ነው። ባለፉት ዐመታት በአገራችን ገበያ ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት አንደኛውና ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ብር አርቲፊሻል በሆነ መልክ በተደጋጋሚ እንዲቀንስ በመደረጉ ነው። ይህ ሁኔታ በተለይም ከተወሰነው የህብረተሰብ የአኗኗር ስልት መለወጥ ጋር በመያያዝ ለኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ሊሆን ችሏል። ከዚህም በላይ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረትና ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የማይመጣጠኑ ባለአምስት ኮከብ ትላልቅ ሆቴልቤቶች መሰራታቸውና ለሰፊው ህዝብ የሚውለውን ምግብና የመቀቀያ ዘይቶችና ቅቤ፣ እንዲሁም መብራትና ውሃ በመጋራታቸው ኑሮን በጣም እንዲወደድ አድርጎታል። ምክንያቱም ለሰፊው ህዝብ የሚቀርቡት  አስፈላጊው ነገሮች ወደ አንድ አቅጣጫ በብዛት ስለሚላኩ ወይም በሆቴል ቤቶች ስለሚገዙ ነው።  2ኛ) የውስጥና የውጭ ገበያውን ለውጭ ኢንቬስተሮች ክፍት ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ከውጭ ኢንቬስተሮች በመምጣት መዋዕለ-ነዋይ ስለሚያፈሱ፣ በዚህም ምንክንያት የተነሳ ኢኮኖሚው ያድጋል የሚል ነው። የውጭ ኢንቬስተሮችን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ ኢንቬስት የሚያደርጉት በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ ሳይሆን፣ በአበባ ተከላና በሌሎች ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች በሚላኩ የጥሬ-ሀብቶች ላይ  ብቻ ነው።  ቴክኖሎጂ ነክ በሆኑ በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ስለማይሰማሩና ፍልካጎታቸውም ስላልሆነ ለውስጡ ገበያ ማደግና የስራ መስክ ለመክፈት ያላቸው አስተዋፅዖ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። የጥሬ-ሀብት ወደ ውጭ የሚላክ ከሆነ ደግሞ ምርቶች ወደ ውስጥ ተፈብርከውና አልቀው ደቀው ተጠርዘው ለአገር ውስጥ ገበያም ሆነ ለውጭ ገበያ አይቀርቡም ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ወደ ውስጥ ብሄራዊ ሀብት(National Wealth) የሚባለው ነገር አይፈጠርም። ብሄራዊ ሀብት ሊዳብር የሚችለው በኢንዱስትሪዎች መሀከል መተሳሰርና መገበያየት ሲኖር ብቻ ነው። ለምሳሌ የማሽን ፋብሪካ ለኢንዱስትሪ ተከላ የሚሆኑ ማሽኖችን እያመረተና ዲዛይን እያደረገ ያቀርባል። ልዩ ልዩ ፋብሪካዎችን ለመትከልና ልዩ ልዩ የረጅም ጊዜና የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸውን ምርቶች እያመረቱ የሚያቀርቡ ካፒታሊስቶች ደግሞ ከማሽን ኢንዱስትሪ ካፒታሊስቶች ማሽኖችን በመግዛት የኢንዱስትሪ ተከላ ያደርጋሉ። በዚያውም መሰረት የስራ መስክ ሲከፈት፣ የሰራተኛውም የመግዛት ኃይል ያድጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሻ ምርቶችም ሆነ ከመሬት ውስጥ የሚወጡ ልዩ ልዩ የጥሬ-ሀብቶች እንዳለ ወደ ውጭ የማይላኩ ከሆነና ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከመጨረሻው ምርት ድረስ እዚያው ፋብሪካ ውስጥ የሚፈበረኩ ከሆነ አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብሄራዊ ሀብት ሊታይና ሊፈጠሩ ይችላሉ ማለት ነው። ስለ አንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገትም በሚወራበት ጊዜ ከእነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች በመነሳት ብቻ ነው።

ከዚህ ሳይንሳዊና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ህግ ሁኔታ ስንነሳ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት ስንመለከት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረገው የአገልግሎት መስኩ ነው። 3ኛ) የመንግስት ሚና መቀነስ የሚል ነው።  በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕምነት የመንግስት ጣልቃ-መግባት የገበያ ኢኮኖሚን ዕድገት ያደናቅፋል። ስለሆነም የአዳም ስሚዝን ሃሳብ የረቀቀውን እጅ(Invisible Hand) ቃል በቃል በመወሰድ ሁሉም ነገር ለገበያ መለቀቅ አለበት ይሉናል። ይሁንና አዳም ስሚዝ (The Wealth of Nations) በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ስለ ስራ-ክፍፍል(Division of Labour)፣ ስለገበያ ትልቅነትና ስለማሺነር አትቷል። እነዚህ ሁሉ ሲጣመሩ ብቻ ነው  የገበያ ኢኮኖሚ ዕውን ሊሆን የሚችለው። ይሁንና አዳም ስሚዝ የሱን ሃሳብ ከማዳበሩ በፊት የውስጥ ገበያን በማዳበር የፍጹም መንግስታት የሚባሉት የተጫወቱትን  ከፍተኛ ሚና ይዘነጋል። መርከንታሊዝም በሚባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው አብዛዎቹ የአውሮፓ መንግስታት በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ለገበያ ኢኮኖሚ መዳበር መሰረት የጣሉት። ሌላው አዳም ስሚዝ የዘነጋው ነገር የእሱ የገበያ ኢኮኖሚ ከመዳበሩ በፊት በአውሮፓ ምድር መንፈስን የሚያድስ የባህል ለውጥ ተካሂዷል። ከዚህም በላይ አዳም ስሚዝ የገበያ ኢኮኖሚ ዛሬ በምናየው መልኩ በመዳበርና በካፒታሊዝም የብዝበዛ ሎጂክ ውስጥ በመውደቅ የዓለምን ኢኮኖሚ ይቆጣጠራል ብሎ አልገመተም። በአንፃሩ ማርክስና ሮዛ ሉክሰምበርግ የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ኃይል በማየት በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዝበዛንና ዘረፋን ለማካሄድ እንደሚችል አመልክተዋልል፤ በዚያውም የዕድገት ፀር ለመሆን ይችላል።  4ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኩባንያዎችና መደብሮች ወደ ግልሀብትነት(Privatization) መዘዋወር አለባቸው።  በዚህ አማካይነት ውድድር ስለሚኖር የገበያ ኢኮኖሚም ዕውን ሊሆን ይችላል ይሉናል። ይሁንና የኢትዮጵያን ሁኔታ ብቻ ስንመለከት ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ በመውጣት ወደ ግል-ሀብትነት የተዘዋወሩት ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂ መሰረታቸው በጣም ደካማ ነበር። ለውድድርና ለፈጠራ የሚያመቹ አልነበሩም። ኢንዱስትሪዎችና ትላልቅ ኩባንያዎች ለወያኔ ካድሬዎች በርካሽ የተሸጡና ለመዝረፍ በሚያመች መንገድ የተዘጋጁ ናቸው። ኢንዱስትሪዎችን የገዙት ደግሞ ከማምረትና ከፈጠራ ጋር የተያያዘ ልምድ ስላልነበራቸው አዳዲሶችን በመክፈትና ያሉትንም በማስፋፋት የስራ መስኮችን ለመክፈት የቻሉ አይደሉም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የመንግስትን ሀብት ለግለሰቦች በቅናሽ መሸጥ ጥቂቶችን ያደለበና ከመንግስት ጋር በመቆላለፍ የአገር ሀብት በከፍተኛ ደረጃ እንዲዘረፍ ያደረገ ነው። በተለይም ዕንቁ የሚባሉ የጥሬ-ሀብቶች በወያኔ ካድሬዎች ቁጥጥር ስር በመውደቃቸው እየወጡ እንዳለ ወደ ውጭ እንዲላኩ ተደርገዋል። አላሙዲ የሚባለው የአገርን ባህል በከፍተኛ ደረጃ ያበላሸውም ከብርቴ ነኝ ባይ የወርቅ ጉድጓድ ማውጫን በመቆጣጠር በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወርቅ እንዳለ ወደ ውጭ በመላክ ራሱንና የካፒታሊስት አገሮችን ለማደለብ በቅቷል። በዚያው መጠንም ህዝባችንና አገራችን በከፍተኛ ደረጃ ለድሀነት ተጋልጠዋል።

ለማንኛውም የዓለም የገንዝበ ድርጅትና የዓለም ባንክ ስለተቅዋም መሻሻል(Structural Adjustment Program) ሲያወሩ የሚነሱት ከክስተት እንጂ መሰረታዊ ከሆኑ የሀብረተሰብ ችግርና ጥያቄዎች አይደለም። የመንግስት ባጀት መጨመር፣ የውጭ ሚዛን መናጋትና የዋጋ ግሽበት የመሳሰሉት፣ እነሱ እንደሚሉን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶች ዋናው ምክንያቶች ኢኮኖሚው በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ካለመመስረቱ የተነሳ ይህ ዐይነቱ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት(Macroeconomic Imbalance)እንደሚከሰት አይነግሩንም። አነሳሳቸውም የአንድን አገር ህብረተሰብ አወቃቀር እንዳለ በመውሰድና ሁሉንም በተናጠል በማየትና በማጥናት የችግሩን ምንጭ ደረጃ በደረጃ መመርመር ሳይሆን በጥቂት ፓራሜትሮች ላይ ብቻ በማትኮር  ነው እነሱ ላይ ብቻ ጥገናዊ ለውጥ ከተደረገ ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ሊመጣ ይችላል የሚሉን። ከላይ እንዳልኩት ይህ ዐይነቱ በክስተት ላይ ብቻ የተመሰረተ አካሄድና መሻሻል ያለውን በሽታ ከማባባሱ በስተቀር ሳይንሳዊ መፍትሄ ሊሰጠው በፍጹም አይችልም። ስለሆነም በእነሱ ዕምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ለገበያ ኢኮኖሚ ወይም ለካፒታሊዝም መዳበር የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማሟላት እንዳለባትና መሰረታዊ ለውጥም መካሄድ እንዳለበት  አይቀበሉም። ይህም ማለተ አካሄዳቸውና ምክራቸው በሙሉ የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ህግና የካፒታሊዝምን ዕድገት የሚቃወም ነው ማለት ነው።  ለምሳሌ የፖለቲካ ተቋማትን መሻሻል፣ የሰውንና የጥሬ-ሀብትን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልጉ ተቋማት ስለመመስረታቸው ጉዳይና፣ በተቀነባበረና በታቀደ መልክ መንግስት ክልዩ ልዩ አካላት ጋር በመሆን ኢኮኖሚውንና ህብረተሰቡን ለማሳደግ ስላለበት መሰረታዊ ጉዳይ አያነሱም። ከዚህም በላይ አንድ አገር በኢኮኖሚ ለማደግ ከፈለገች በታቀደ መልክ ከተማዎችና መንደሮች ስለመገንባታቸውና፣ እነዚህም በልዩ ልዩ የመመላለሻ መንገዶችና መስመሮች መያያዝ ስላለባቸው ጉዳይ በፍጹም አያነሱም። ቦታና ጊዜ(Space & Time) የሚለው አስተሳሰብ በአስተሳሰባቸው ውስጥም በፍጹም የለም።  በእነሱ ዕምነት ሁሉም ነገር ለገበያው ከተለቀቀ የሚታዩት ችግሮች በሙሉ ይፈታሉ ይሉናል። ሰለሆነም የዓለም የገንዘብ ድርጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክር የአንድን አገር ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ላይ እንዲገነባ የሚያደርግ አይደለም። ግልጽነት ያለውና ቁጥጥር የሚደረግበት የገበያ ኢኮኖሚም ኦርጋኒክ በሆነ መንገድ መገንባት እንዳለበት፣ ለዚህ ደግሞ ሁለ-ገብ ዕውቀት ተግባራዊ መሆን እንዳለበትና፣ ሰፊው ህዝብም መማር እንዳለበት አይቀበሉም። በእነሱ አስተሳሰብ የነቃና ያወቀ ህዝብ አያስፈልግም። ይህ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቀው የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታምና ጥራዝ-ነጠቅ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም ደሀ ህዝብ እንደ አሸን ይፈለፈላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ልቅ በሆነ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የባህልና የስነ-ልቦና ውድቀት ይከሰታል። በተጨማሪም ማፊያዊ ተቋማት በየቦታው በመቋቋም በቀላሉ ሊታለል የሚችለውን የህብረተሰብ ክፍል ማታለልና ማስፈራራት ይችላሉ። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከስላሳ ዓመት በላይ በሚያስቆጥር ጊዜ ውስጥ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል የአጭበርባሪነትና የማፊያ አስተሳሰብን አዳብሯል። ትንሽ ገንዘበ ለመዝረፍ ሲባል አንዳንድ ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜያቸው ገፋ ያሉትን በአሰቃቂ መንገድ መግደል እንደዋና ተግባርና ልምድ ሊወሰድ ችሏል። የጾታ ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቷል። መንግስትና አገዛዙ ይህንን እንደተራ ነገር በመቁጠር በፍጹም ቁጥጥር አያደርጉም። ከዚህ በተጨማሪም የስራ ዕድል ለማግኘት የማይችለውም ወጣት ወደ ጨአት መቃምና ወደ ሌሎች የዕፅ ሱሰኘንት እንዲያመራ ለመገደድ በቅቷል። የወጣት ሴተኛ አዳሪዎችም ቁጥርና የግብረ-ሰዶማዊነትም ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል። በተለይም በዕርዳታ ስም የሚመጡ የውጭ አገር ሰዎች ግብረሰዶማዊነትን በከፍተኛ ደረጃና በፍጥነት እያስፋፉት ይገኛሉ። በዚህ መልክ የካፒታሊስት አገሮች ባለፉትት 30 ዓመታት በሁሉም አቅጣጫ የባህል ጦርነት በማካሄድ ህዝባችንን አቅመ-ቢስ ለማድረግ በቅተዋል። የወያኔ አገዛዝና ዛሬ ደግሞ ኦሮሞው የአቢይ አገዛዝ ከአሜሪካንና ከተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ጋር በማበር በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ጦርነት ከፍቷል። በዚህ መልክ ኢትዮጵያ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ስር በመውደቅ እሴቷና ልዩ ልዩ የመተጋገዝና የማህበራዊ ባህሎቿ መውደም አለባቸው።

በአጠቃላይ ሲታይ ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ የሆነውን እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት መሰረቱ ኒዎ-ሊበራሊዝም ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራሊዝም ኢኮኖሚ ፖሊሲ በካፒታሊዝም የዕድገድት ታሪክ ውስጥ እስከ 1980ዎቹ ዓመታት ድረስ በፍጹም ተግባራዊ አልሆነም። ዛሬም ቢሆን አይደረግም። በእርግጥ ጀርመን የአንደኛውን ዓለም ጦርነት ከተሸነፈች በኋላ ካሳ እንድትከፍል በመገደዷ በዚህም የተነሳ ከኤክስፖርት የምታገኘውን አብዛኛውን የውጭ ምንዛሪ ለእንግሊዝና ለፈረንሳይ ትከፍል ነበር። በዚህ ዐይነቱ የአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ በጊዜው ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ አጥ ሊፈጠር ችሏል። ይህም በራሱ ለፋሺዝም መነሳት  አንደኛው ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ በተረፈ በሌሎች የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ እንደዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም ተግባራዊ አልተደረገም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት የነበረውን ሁኔታ በመተው፣  ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት መንግስታት በታላቁ የእንግሊዝ ኢኮኖሚስት በኬይንስ የቀረበውን ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ነው ሁለ-ገብ በሆነ መንገድ አገራቸውን መገንባት የቻሉት። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአገራችን ምድር አይታወቅም። ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲማሩ አይደረግም። ከዚህም በላይ ልዩ ልዩ በትቻታዊ መልክ የቀረቡትን ግሩም ግሩም ስለ ዕድገትና ስለፀረ- ዕድገት የሚያትቱ መጽሀፎችንም አይማሩም። ስለሆነም የኢኮኖሚ ቲዎሪን በሚመለከት በአገራችን ምድር ከፍተኛ ክስተት አለ። አንድን ቀኖናዊ መንገድ በመከተል ብቻ አገራችንና ህዝባችንን ገደል ውስጥ እየከተቷቸው ነው ማለት ይቻላል።

ወደ አቢይ አገዛዝ ስንመጣ ይህ ሁኔታ ቀጠለ እንጂ በፍጹም አልተሻሻለም። በአካባቢው የተሰበሰቡት የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ የሆነውn የግርማ ብሩን ሁኔታና፣ የውጭ ንግድ አማካሪ የሆነውንና በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትን እንደቴሌና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉት የግዴታ ወደ ግል-ሀብትነት መዘዋወር አለባቸው፣ በተለይም ደግሞ የውጭ ኢንቬስተሮች ይሳተፉበት እያለ የሚወተውተውን የማሞ ምህረቱን የዕውቀት ደረጃ ስንመለክት ያው እንደምናየው ስራቸውንና ውጤታቸውን የአገራችን የኢኮኖሚና የድህነት ብዛት፣  እንዲሁም የዋጋ መናር ያረጋግጣሉ። እንደዚሁም በገንዘብ ሚኒስተር ውስጥ በሚኒስተር ዲኤታ ስም የተቀመጠውና ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈለው እንደ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የመሳስለው  የአገራችንን ኢኮኖሚ ካለበት በፍጹም ፈቀቅ ማድረግ አላስቻሉትም። ይባስ ብሎ ድህነቱና በውጭ ኃይሎች ስር እንድንወድቅ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት ነው አገራችንና ህዝባችንን መቀመቅ ውስጥ የከተቷቸውና የሚከቷቸው። በ2020 ዓ.ም በዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ መሪነት የአገራችንን ኢኮኖሚ ካለበት ማነቆ ውስጥ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ሊያወጣው ይችላል ተብሎ የታሰበ  „Home Grown Economy“  የሚል ረቅቆ ቀርቦ ነበር። ይህንንም በሚመለከት ሆም ግሮውን የተባለበትን ምክንያት ስላልገባኝ የራሴን ሰፋ ያለ ግምገማ እንደዚህ በ2020 ዓ.ም አቅርቤ ነበር። ለማናኛውም የሆም ግሮውን ኢኮኖሚ የሚባለው ፖሊሲ እስካሁን ድረስ ያመጣው ውጤት ምን እንደሆን በፍጹም አይታወቅም። የምናውቀው ነገርና ስታትስቲክሶችም እንደሚያረጋግጡልን ትላልቅ ሆቴል ቤቶች ከመሰራት በስተቀር ለኢኮኖሚው ዋና መሰረትና አንቀሳቃሽ የሚሆኑ ነገሮች ተግባራዊ እንዳልሆኑ ነው። ፖሊሲውንና ሀተታውንም ስንመለከት አቀራረቡ የታወቀውን የቴክኖራቲክ አቀራረብ እንጂ ለአገራችን ኢኮኖሚ ዋናው ምክንያት የሆኑትን ደረጃ በደረጃ የሚያትት አይደለም። በተለም በወያኔ ጊዜ ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንዳችም ቦታ ላይ አይጠቅስም። እንዲያውም ሀተታው በወያኔ ጊዜ የሚያስደንቅ ዕድገት እንደታየ ነው የሚነግረን። ታዲያ ይህ ከሆነ ሆም ግሮውን የሚባል ፖሊሲ ለምን አስፈለገ?

ያም ሆነ ይህ እነዚህ ወጣት ኢኮኖሚስቶች በአንድ ወቅት በዓለም ባንክ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩና ዓለም ባንክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያስፋፋው ድህነት ውስጥ የተካፊሉ ናቸው። በዚህም ከፍተኛ ልምድ ያካባቱ ናቸው። ጆን ፐርኪን የሚባለው ለጥቂት ዐመታት በዓለም ባንክ ውስጥ በብዙ መቶ ሺህ ዶላር የሚቆጠር ደሞዝ እየተከፈለው ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቶት በሚሰራበት ዘመን ያየውን ልምድ፣  ህሊናዬ  በዚህ መልክ ለመቀጠል አይፈቅድልኝም በማለት ስራውን ለቆ ከወጣ በኋላ „Economic Hit Men“  በማለት የፃፈው መጽሀፍ ውስጥ በዓለም ባንክ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢኮኖሚስቶች የአጭበርባሪነት ባህርይ እንደሚታይባቸውና፣ ዋናው ሚናቸውም የአንድን አገር ኢኮኖሚ ከታች ወደላይ ኦርጋኒክ በሆነ መልክ መገንባትና ጤናማ ህብረተሰብ መመስረት ሳይሆን፣ በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ ነው የሚለውን ላነበበ ሰው ሊገንዘብ ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም እዚያው ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩና፣ ሌሎችም ከቅርብ ሆነው ይከታተሉ የነበሩ ትችታዊ መጽሀፎችን በመጻፍ የዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የእነ ዓለም ባንክን የተሳሳተ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሚገባ አሳይተዋል። ችግሩ እንደኛ አገር ያሉ ምሁሮች ትችታዊና አገርን ገንቢ የሆኑ መጽሀፎችን ማንበብና ራሳቸውን መጠየቅ በፍጹም አይችሉም። አለርጂ ያለባቸው ይመስል ከትችታዊ አስተሳሰብ በብዙ ሚሊዮን ማይሎች ርቀው የሚገኙ ናቸው። ተቀባይነትን ካገኘ ዶግማ መላቀቅ የለብንም የሚል ነው አስተሳሰባቸው።

ለማንኛውም ማሞ ምህረት የአቢይ አህመድ የቅርብ አማካሪው ከሆነና ህዝባችንና አገራችን የሚፈልጉትንና የሚጠይቁትን ነገሮች ወይም መሻሻሎች ካላመጣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ቢሆን ምን ነገር ሊሰራ ይችላል? ሌላው መነሳት ያለበት ጥያቄ አንድ ሰው የብሄራዊ ባንክ ገዢ ሆኖ ከመሰየሙ በፊት በባንኩ ዘርፍ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የሰራ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም ሰለሞኔቴሪ ቲዎሪ መጽሀፎችንና ሳይንሳዊ ጽሁፎችን የጻፈ መሆን አለበት። በተለይም የካፒታሊዝምን ዕድገት የተከታተለና፣ ገንዘብ ከታች ወደላይ በኮሞዲት ፎርም እንዴት እንደሚሰራና፣ ዛሬ በምናየው መልክ በወረቀት ገንዘብ(Fiat Money or Paper Money) እንደተተካና ምክንያቱስ ምን እንደሆነ የተከታተለ መሆን አለበት። እስከ አስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በአብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በሳንቲም መልክ የቀለጠና የነገስታት ፎቶ ወይም ማህተም ያለበት የወርቅና የብር ገንዘብ ነበር በኢኮኖሚው ውስጥ ይሽከረከር የነበረው። ወርቅ የተፈጥሮ ሀብት እንደመሆኑ መጠንና እንደልብም ስለማይገኝ እያደገና እየተወሳሰበ በመሄድ ላይ ካለው የካፒታሊስት ምርታዊ ክንዋኔና የንግድ እንቅስቃሴ ጋር ሊጓዝ የሚችል ገንዘብ ማቅረብ አለታቸለም ነበር። በጊዜው በኢኮኖሚ ምሁራን የቀረበው አስተሳሰብ ማዕከላዊ ባንክን በመፍጠር በወርቅ የተደገፈ የወረቀት ገንዘብ ማተም ነበር። የወረቀት ገንዘብ እንደልብ ማተም ሲቻል፣ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታም ካለምንም ችግር በቀላሉ ማመላለስ ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን የንግድና የምርትን እንቅስቃሴንም ያፋጥናል። በዚያው መጠንም የካፒታል ክምችት ይዳብራል። ይሁንና ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተለይም የቅኝ ግዛቶችን ማስተዳደር ያቃጣት እንግሊዘ በወርቅ ከሚደገፍ ገንዘብ ይልቅ የወረቀት ገንዘብ በማተም ይህም ህጋዊ ገንዘብ(Legal Tender) ለመሆን በቃ። በአሁኑ ወቅት በወርቅ የሚደገፍ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የለም፡፟፡ ይሁንና አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች በወርቅ የሚደገፍ የወረቀት ገንዘብ መታተም እንዳለብት ያትታሉ። ምክንያቱም ይህ ዐይነቱ አካሄድ ገንዘብን አስተማማኝ ስለሚያደርገው መንግስታትም እንደፈለጋቸው የወረቀት ገንዘብንም ከማተም ይታገዳሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ብዙ አገሮች፣ በተለይም እንደ ራሺያና ቻይና የመሳሰሉት ከዶላር በመላቀቅ በራሳቸው ገንዘብ በመገበያየት፣ ብሪክስ የሚባለውን አዲስ ከረንሲ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው። በዚህም መልክም የዶላርን የበላይነት ለመዋጋት ይቻላል ብለው ይገምታሉ።

ለማንኛውም የማሞ ምህረቱ የማዕከላዊ ባንኩ ገዢ መሆን ያለውን የባንኩንም  ችግር በፍጹም አይቀርፈውም። ወንድማችን እንዳለው አዲሱ የባንክ ገዢ በእነ ዓለም የገንዝበ ድርጅት በመመከር የባሰውኑ ገንዘቡን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር የባሰ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር፣ አሁን ካለው የብርና ዶላር ልውውጥ ሁኔታ አንድ ዶላር ለመግዛት 53 የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ ሲያስፈልግ፣ ወደፊት ልውውጡ ወደ 70ና 80 የኢትዮጵያ ብር ከፍ ሊል ይችላል ማለት ነው። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና ሌሎች ኤክስፐርቶችም ከፍተኛ ግፊትና ውትወታ ስለሚያደርጉ ሁኔታው እየተበላሽ እንደሚሄድ አያጠራጥርም። ከላይ ለማተት እንደሞከርኩት፣ የኢትዮጵያን ብር በየጊዜው ዝቅ ማድረግ የመግዛት ኃይሉን ከማዳከምና ሰፊውን ህዝብ ከመጉዳት በስተቀር የሚያመጣው ጠቀሜታ በፍጹም የለም። የአንድን አገር ገንዘብ በዚህ መልከ በተከታታይ በመቀነስ የአንድን አገር ኢኮኖሚ በፍጹም ማሳደግ አይቻልም። እስካሁን ድረስ እንደታየው ከኢትዮጵያ መንግስት በስተቀር በዚህ መልክ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ምክር በመቀበል የአገሩን ገንዘብ በተከታታይ ዝቅ ያደረገ አንዳችም የአፍሪካ አገር አይገኝም። በዚህ ረገድ ልዩ ዐይነት ተሰጥዖ ያለን የኢትዮጵያ መንግስትና የአገር ውስጥ አማካሪዎቹ ናቸው። ይህ በእንደዚህ እንዳለ አሁን ደግሞ የባንኩን ዘርፍ ለውጭ አገር ባንኮች ክፍት መደረግ አለባቸው የሚለው አካሄድ እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው። የውጭ እንቬስተሮች የባንኩ ዘርፍ ክፍት ከሆነላቸው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርና ኦይሮ ሊያመጡ ይችላሉ የሚለው አስተሳሰብ በጣም የዋህነት ብቻ ሳይሆን አላዋቂነትንም ነው የሚያሳይ። የባንክንም ዋናም ሚና ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት ነው። የባንኩ ዘርፍ ገንዘብ በቁጠባ መልክ የሚቀመጥበት ብቻ ሳይሆን፣ ባባንኩ ዘርፍ አማካይነት ነው ገንዘብ ከአንድ ሰው እጅ ወደ ሌላ፣ ከአንድ አምራች ወደ ሌላ አምራችና ነጋዴ የሚተላለፈው። ይህ ብቻ ሳይሆን የባንኩ ዘርፍ ለልዩ ልዩ ነገሮችና የመዋዕለ-ነዋይ ገንዘብ የሚያበድር ዘርፍ ነው። ታዲያ የውጭ ባንኮች በአገራችን ባንኮች ቢሳተፉ ሚናቸው ምን ይሆናል? የአገራችንን ባንኮችና የኢኮኖሚውን ዘርፍ ቀልጣፋ የማድረግ ኃይል ይኖራቸዋል ወይ? ለአጠቃላዩ የአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገትስ አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ ይችላሉ ወይ? ትርፍ ካተረፉስ ትርፉን እንደገና እዚያው አገር ቤት ውስጥ ኢንቬስት ያደርጋሉ ወይ? ወይስ ወደዶልራና ኦይሮ እየለወጡ ወደ አገሮቻቸው ባንኮች ውስጥ ያስተላልፏቸዋል? እነዚህ ሁሉ መብራራት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ መሰረታዊና አጭር ሀተታ ስንነሳ የማሞ ምህረቱ የማዕከላዊ ባንክ ገንዘብ ዋና ኃላፊ መሆን የአገራችንን ኢኮኖሚ  በአጠቃላይና፣ የባንኩን ዘርፍ ችግር በተለይ መሰረታዊ በሆነ መልክ ሊፈታው በፍጹም አይችልም። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

ማሳሰቢያ፤ እነዚህ የመሳሰሉ ጥናቶች የብዙ ሰዎችን ተሳትፎ ይጠይቃሉ። በአንድ ሰው ጥረትና ትግል ብቻ ችግሩን መረዳትና ማስረዳትም በፍጹም አይቻልም። እንደምከታተለው ከሆነ በአብዛኛዎች አገሮች ውስጥ ብዙ ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው ምሁራን አንድ ላይ በመሆን ነው በተለይም ከውጭ የሚመጣውን ግፊትና የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚዋጉት። አብዛኛዎቹ በተቋም የሚደገፉና ሃሳብ ለሃሳብ እየተለዋወጡ ነው የሚሰሩት። ወደ አገራችን ስንመጣ አብዛኛዎቻችን ክሪቲካል አመለካከት ለማዳበር በፍጹም አልቻልንም። ከውጭ የሚመጣውን ፖሊሲ እንደቀኖናዊ አስተሳሰብ በመውሰድ ብቻ እሱን እየመላለሱ ተግባራዊ ማድረግ ሆኗል የያዝነው ፈሊጥ። በዚህ መልክ የአገራችንን ውድቀት እያፍጠን ነው። ከዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ መላቀቅና ክሪቲካል አስተሳሰብ ማዳበር ለአገርና ለህብረተሰብ ዕድገት በጣም አስፈላጊ ነው። ካለበለዚያ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ነው።

ጓደኛዬ የላከልኝን ይህንን በጣም ጠቃሚ መልዕክት አንብቡ!

How To Destroy A Country.

Very true…

At the entrance gate of a university in South Africa

the following message was posted for contemplation

„Destroying any Nation does not require the use of Atomic Bombs

Or the use of long-range missiles. It only requires lowering the quality of

Education and allowing cheating in the examinations by the students”

Patients die at the hands of such doctors…

Buildings collapse at the hands of such engineers…

Money is lost at the hands of such economists & accountants…

Humanity dies at the hands of such religious scholars…

Justice is lost at the hands of such judges…

እዚህ ውስጥ ያልተካተተ!

Rulers too are the products of such kinds of education system…

“The collapse of education is the collapse of the nation”