[gtranslate]

ኋላቀር አስተሳሰብ ባላቸውና  በአረመኔዎች የሚመራ ምስኬን ህዝብና አገርበሚል አርዕስት ስር 24.04.2022 ያቀረብኩትን

ሰፋ ያለ ጽህፍ አስመልክቶ ከአቶ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ  ቦርከና በሚባለው ድረ-ገጽ ላይ ለወጣው ትችት መልስ!  

                                                                       ፈቃዱ በቀለ(/)

ሰኔ 20 2022

በመጀመሪያ ደረጃ አቶ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅን ለሰጠው ወይም ላቀረበው ትችት ሳላመሰግነው አላልፍም። አንድ እንደዚህ ዐይነት አገርንና አገዛዝን የሚመለከት ሰፋ ያለ ጽሁፍ በሚቀርብበት ጊዜ ጽሁፉን ያነበቡ ሰዎች በአተናተን ዘዴው ያልረኩ ከሆነ ወይም “በመረጃ ያልተደገፈ” ከመስላቸው ትችት የመስጠት መብት አላቸው።

ይህን ካልኩኝ በኋላ አቶ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ ሲጀምር ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ በምን ሙያ እንደሰለጠነ ለማወቅ በኢንተርኔት ያደረጉት የፍለጋ ሙከራ አልተሳካልኝም ይላል። አቶ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ ሀቀኛ ቢሆን ኖሮ የጉጉል ሰርች ማሽን ላይ በእንግሊዘኛ ፈቃዱ በቀለ የሚለውን ስም ቢሰጥ ኖሮ ስለእኔ ማንነት ለማወቅ የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት በቻለ ነበር።

ለማንኛውም ለእኔ ለማወቅ ከፈለግህ የፖለቲካ ትግል የጀመርኩት 23 ዓመት ዕድሜ በነበርኩበት ጊዜ ሲሆን፣ እንደአጋጣሚ ሆኖ ጀርመን ከመጣሁ በኋላ የተዋወቁት ከማርክሲዝም የፖለቲካ፣ የህብረተሰብና የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ጋር ነው። በመጀመሪያው ወቅት የማርክሲዝምን ቲዎሪ ለመረዳት ችግር ቢኖርብኝም ቀስ በቀስ ግን መሰረተ-ሃሳቡን ለመገንዘብ ችያለሁ። አንድን አስተሳሰብ ብቻ ትክክል ነው ብዬ ከመጀመሪያውኑ ቀኖናዊ አስተሳሰብ ጭንቅላቴን እንዳይዘው በመፍራት ከተለያዩ አቅጣጫዎች፣ በተለይም የከበርቴው የፖለቲካ ቲዎሪ፣ የሰብአዊነት ቲዎሪ ከሚባሉት ጋር በመተዋወቅ የምዕራብ አውሮፓን የህብረተሰብ አስተዳደግና አወቃቀር፣ በተለይም ደግሞ የካፒታሊዝምን ዕድገት በመጠኑም ቢሆን ለመገንዘብ ችያለሁ። በጊዜው ደግሞ በተለይም ካፒታሊዝም እንዴት እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ሊደርስ ቻለ? ምክንያቶችስ ምንድናቸው? ሌሎች አገሮች ለምን እንደምዕራብ አውሮፓ አገሮች የካፒታሊዝምን  ስርዓት ሊጎናጸፏ አልቻሉም? ለምንስ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ የተሟላ ዕድገት ማዳበር አልቻሉም? እየተባለ ሰፊ ጥናትና ክርክር ይካሄድ ስለነበር ነገሩን ለመረዳት ከጓደኞቼና ከእኔ የተሻለ ግንዛቤ ካላቸው የነቁ ሰዎች ጋር ቁጭ ብዬ በማጥናት ቀሰ በቀስ ለካፒታሊዝም ዕድገት ምክንያቶች የሆኑትን ነገሮች ለመረዳት ችያለሁ ብል የምሳሳት አይመስለኝም። በአጭሩ የፖለቲካን ትግል የተቀላቀልኩት ትላንት ሳይሆን ከሰላሳ ዓመት በፊት ሲሆን፣ በእነዚህ ወርቃማ ዓመታት ውስጥ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናዬን ለማጎልመስ ከተለያዩና በጣም የዳበረ ልምድና አስተሳሰብ ካላቸው ድርጅቶች ጋር በመስራት ስለፖለቲካ ምንነት፣ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? የሰው ልጅስ በምን መልክ ነው የሚታየው? ስለፍትህና ስለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ምንነትና ስለመንግስት ሚናና በመንስ መልክ መዋቀር እንዳለበት፣ ወዘተ. … በማለት የሚነሱትን ጥያቄዎችና የሚካሄዱትን ጥናቶች ውስጥ በመሳተፍ አያሌ ነገሮችን ለመማርና መንፈስኔን ለመኮትኮትና ለማጠንክር ችያለሁ ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ከዚህ በመነሳት በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሁለ-ገብና አስተማማኝ፣ እንደዚሁም ተከታታይነትና ዘላቂነት ያለው ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ህብረተሰቡ በቁንጽል አስተሳሰብ መዋቀር ያለበት ሳይሆን ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መልክ መዋቀር እንዳለበት ለመገንዘብ ችያለሁ። በእርግጥም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተደረገውን እልክ አስጨራሽ የህብረተሰብ ግንባታ ትግል ስንመረምር በጊዜው የተገለጸላቸው ምሁራን ሁለንታዊ የሆነውን ሳይንሳዊ፣ የፍልስፍናና የቲዎሪ መንገድ ባይከተሉ ኖሮ የምዕራቡ ካፒታሊስት ስርዓት ዛሬ በምናየው መልክ ውስጣዊ ኃይል ማግኘት ባልቻለ ነበር። ይህ ማለት ግን ከሶስት መቶና ከአራት መቶ ዓመታተ በፊት የነበሩ ምሁራን ለእንደዚህ ዐይነቱ የካፒታሊስት ስርዓት የታገሉ ናቸው ማለት ሳይሆን ዋና ምርምራቸውና ዓላማቸው በጊዜው ከሰፈነው አስከፊና ስርዓት በመነሳት የሰው ልጅ  ጭንቅላቱን ክፍት በማድረግ ጤናማና ፍትሃዊ ያለበት ስርዓት ለመመስረት በማሰብ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰብ ዕድገት ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የማያቋርጥ ምርምር አስፈላጊ መሆናቸውን በመረዳት ሳያስቡት የኋላ ኋላ ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ሊወጣ የቻለበትን መንገድ አመቻችተዋል ማለት ይቻላል። ይሁንና የህብረተሰብ ግንባታ ሂደት በተፈለገው መልክ ይዞ የሚጓዝ ሳይሆን በየጊዜው በሚነሱ የተለያዩ ኃይሎች ፈተና ውስጥ ስለሚወድቅ መስመሩን እንዲስት ሊደረግ ችሏል።  እነሱ ባቀዱትና በፈለጉት መንገድ ካፒታሊዝም ፍትሃዊና ከብዝበዛ ነፃ በሆነ መልክ ሊዋቀር አልቻለም።

ለማንኛውም የአውሮፓውን የባህልና የህብረተሰብ ታሪክ ዕድገትና ለውጥ ለመረዳት መጣሬ እንደኛ በመሳሰሉ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽና የተሟላ ዕድገት ለምን ሊፈጠር እንዳልቻለ አነሰም በዛም ለመረዳት ችያለህ ብል ግብዝነት አይሆንብኝም። ከዚህም በሻገር ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን የኃይል አሰላለፍ ለውጥ በማጥናት በአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የምዕራቡ ካፒታሊዝምና አፈቀላጤዎች፣ ማለትም እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ(WB)  የመሳስሉት የዓለም አቀፍን ካባ የተከናነቡ ተቋማት አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ አገሮች ኢ-ሳይንሳዊና ፀረ-ፍልስፍና የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ በማስገደድ የእነዚህን አገሮች ህብረተሰብ ለማዘባራረቅ እንደቻሉና የውንብድና ስርዓትና ፈሺሽታዊ አገዛዞች እንዲሰፈኑ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ለማጥናት ሞክሬያለሁ። በአጭሩ ስለኢምፔሪያሊዝም ምንነትና የሶስተኛው ዓለም አገሮች ጤናማና ፍትሃዊ ስርዓት እንዳይገነቡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ፣ በተለይም በ1950ዎቹና 60ዎቹ ዐመታት በአንዳንድ የአሜሪካን ሶሶዮሎጂቶችና ኢኮኖሚስቶች የዳበረውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋውን ፀረ-ሁለገብ ቲዎሪ ሳይገነዘቡ ስለዕውነተኛ ነፃነት ምንነትና አተረጓጎም መታገል ስለማይቻል ወደ ሰላሳ ዐመታት ያህል በፀረ-ኢምፔሪያሊዝም ጎራ ውስጥ በመሰለፍ በተለይም በኢትዮጵያው ማህበረሰብ ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ ችያለሁ። ጽሆፎችን በውጭ አገር በሚገኙ ድረ-ገጾች ላይ ብቻ ሳይሆን በጦቢያና በአውራምባ፣ እንዲሁም እንደ ሪፖርተር በመሳሰሉት መጽሄቶችና ጋዜጣዎች ላይ በመታተም ለአንባቢያን አቅርቤያለሁ። ስለሆነም በዚህ ዐይነቱ የትግል ሂደት ውስጥ በማለፌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ማግኘት ያልቻልኩትን ዕውቀት ማግኘትና የአስተሳሰብ አድማሴንም ለማሳድግ ችያለሁ ብዬ እገምታለሁ።

በአጠቃላይ ሲታይ የህብረተሰብን ዕድገት ለመረዳት የመረጥኩት የኢኮኖሚክስ ሳይንስ የሚለውን ሲሆን፣ በተለይም ከማርክሲስት የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ጋር መተዋወቄ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰጠውን በኒዎ-ክላሲካልና በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ላይ የተመሰረተውን የትምህርት አስተጣጥ ዘዴ ትችታዊ በሆነ መልክ እንድገመግመው አስችሎኛል። በሌላ ወገን ደግሞ የግዴታ ዲግሪዬን ለመጨበጥ ስለፈለግሁኝ  የኒዎ-ክላሲካልንም ሆነ የኬይንስን የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችን የግዴታ መከታተልና ፈተናም መጻፍ ነበረብኝ። ከሚክሮና ከማይክሮ ኢኮኖሚክስ ባሻገር፣ የግዴታ የሁኑትንና ፈተናም መታለፍ ያለባቸውን እንደስታትስቲክስ፣ እንደማቲማቲክስ፣ ሊንያር አልጄብራና አናሊይሲስ የመሳሰሉትን፣ እንደ ቡክ-ኪፒንግና፣ እንደ ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚክስ፣ ስለማናጀሜንትና ሌሎችንም አጠቃላይ ኮርሶች በጥብቅ በመከታተልና ፈተናዎችንም በማለፍ፣ ባችለሬን ካጠናቀቁኝ በኋላ ማስትሬት ዲግሪዬን ለመስራት ችያለሁ። በማስትሬት ኮርስ ላይ የግዴታ ትኩረት የሚሰጠው ስለማክሮ ኢኮኖሚክስ ቲዎሪና ማክሮ ኢኮኖሚክስ ፖለቲካ፣ ስለቀረጥ አሰባሰብና ስለበጀት አጠቃቀም፣ ከዚህም በላይ እንደምርጫ ስለ ዕድገት ኢኮኖሚክስ ወይም ዴቬሎፕሜንት ኢኮኖሚክስ ኮርስ በመውሰድና ፈተናዎችን በማለፍ በበጣም ጥሩ ውጤት ካለፍኩኝ በኋላ የዶክትሬት ስራዬን ለመስራት ዕድል አጋጥሞኛል። ጀርመን አገር ዶክትሬት ዲግሪ ለመጻፍ የግዴታ በጣም ጥሩ ውጤት ማግኘትና፣ በተጨማሪም ቴሲስ መጻፍ ያስፈልጋል። የመረጥኩትም “ለምን በኢትዮጵያ ምድር ካፒታሊዝም ለማደግ አልቻለም?” የሚለውን አርዕስት ሲሆን፣ ዶክትሪት ዲግሪዬን በዚሁ ላይ በማትኮር የበለጠ በጥልቀት እንድመራመር ዕድል ሰጥቶኛል። በተለይም በጊዜው ስለአፍሪካና ስለላቲን አሜሪካ አገሮች ኋላ መቅረት ሰፋ ያለ ክርክር ይደረግ ስለነበር፣ ከእነዚህ አገሮች ምሁራን የሚሰነዘሩትን ገንቢና ትምህርታዊ አስተሳሰቦች ጋር ለመተዋወቅ ችያለሁ። ከዚህም ባሻገር ለማነፃፀር እንዲመች የግዴታ የአውሮፓውን የህብረተሰብና የባህል ዕድገት ኋላ መለስ ብዬ እንድቃኝና እንድመራመር ዕድል በማግኘቴ የአገራችንን ኋላ-ቀርነት በዚህ መነጽር ለመረዳት ሙከራ አድርጌአለሁ ለማለት እደፍራለሁ። የመጨረሻም መጨረሻም ከአምስት ዓመት ጥናትና ምርምር በኋላ የ480 ገጽ መጽሀፍ በመጻፍና ስራዬን ዲፌንድ በማድረግ በበጣም ጥሩ ውጤት በማግኘት ለማለፍ ችያለሁ። የዶክትሬት ጥናቴም በአጠቃላይ ሲታይ ዴቬሎፕሜንት ኢኮኖሚክስ በሚለው ዙሪያ ሲሆን፣ በተለይም የኢትዮጵያን የህብረትዘስብ አወቃቀርና የአመራረት ዘዴ፣ ስለስራ ክፍፍል አለመዳበርና ለገበያ አለማደግ ጉዳይ፣ እንዲሁም በከተማዎች የሚገለጽ ህብረተሰብአዊ አወቃቀር ስላለመኖሩ ጉዳይ፣ በዚህ ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥናት ለማድረግ ችያለሁ። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በተለይም ዴቬሎፕሜንት ኢኮኖሚክስ የሚለው ዘርፍ በተሟላ መልክ ግንዛቤ ሊያስገኝ የሚችለው። የዶክትሬት ስራዬንም ከአጠናቀቅኩኝ በኋላ በፍሪ ዩኒቨርሲቲ በርሊን፣ እንደዚሁም በዚህ ከተማ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ኮሌጆች ውስጥ በፓርት ታይም ተቀጥሬ ለማስተማር ዕድል አጋጥሞኛል። በተለይም ስለዓለም አቀፍ ንግድ፣ ስለዕዳ፣ ስለኋላቀርነትና፣ ሰለ አይኤምፍ(IMF) የኢኮኖሚ ፖሊሲና አሉታዊ ውጤቱ፣ ከዚህ የተለየ ፖሊሲ እንዳለና የእነ አይኤምኤፉ(IMF)  ፖሊሲ የተሳሳተና ድህነትን ፈልፋይ እንደሆነ ለማስተማር ችያለሁ። ይህንን አስመልክቶ አያሌ ጥናቶች በመጻፍ ለድረ-ገጾች አቅርቢያለሁ። ጽህፎቹም በጀርመንኛ፣ በእንግሊዘኛና በአማርኛ ሲሆኑ፣ እነዚሁም በድረ-ገጼ ላይ በዝርዝር ተቀምጠዋል። www.fekadubekele.com የሚለውን ድረ-ገጽ ብትመለከት የተለያዩ ጽሁፎቼን ልትመለከትና ለማንበብ ትችላለህ። በተጨማሪም  „African Predicaments and the Method of Solving them Effectively“ የሚል መጽሀፍ በመጻፍ ለአንባቢያን አቅርቤያለሁ። ከዚህም በላይ በአማርኛ ስለካፒታሊዝም ምንነትና አጸናነስ መጽሀፍ በመጻፍ ዕውቀትኔ ለማጋራት ችያለሁ። ይህ ብቻ ሳይበቃ የራሴን የዩቱቭ ቻናል በመክፈት ትምህርት አዘል ሀተታዎች ለመስጠት ችያለሁ። የዩቱቭ አርዕስቱም „Ethiopian Renaissance“ የሚል ነው። የአማራኛን ቋንቋ በጀርመን ምድር ለማስተዋወቅ በሚል ከአምስት ዓመት ስራ በኋላ ከባለቤቴ ጋር በመሆን የጀርመን-አማርኛና፣ የአማርኛ ጀርመንኛ መዝገበ-ቃላት ለመጻፍ ችያለሁ። ከዚህ በተረፈ አሁንም ቢሆን በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ስለ ስልጣኔ፣ ስለግሎባላይዜሽንና በተለይም ደግሞ የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን የጥሬ-ሀብትና ገንዘብ በመጠቀም ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ እንዴት ከድህነት ሊላቀቁ እንደሚችሉና፣ አነሰም በዛም ከውዝግብ ነፃ የሆነ ህብረተሰብ ለመመስረት እንደሚችሉ በሌክቸር መልክ ገለጻ እሰጣለሁ። ለዐይነተኛና ለመሰረታዊ ለውጥ ደግሞ የመንግስት አወቃቀር መለወጥና ስልጣን ላይ የሚወጡም ኃይሎች የግዴታ ሁለ-ገብ ዕውቀት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሞራላዊ ብቃት እንዲኖራቸው እንደሚያስፈልግ በትምህርት መልክ በመሰጠት ላይ እገኛለሁ።

ወደ ትችትህ ልምጣ። በመሰረቱ የአጻጻፌን ስልት የተረዳህ አልመሰለኝም። ለማሳየት የሞከርኩት ስልጣኔና ምሁራዊ እንቅስቃሴ በጭንቅላት አቀራረጽና መዳበር  ላይ ያላቸውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳየት ሲሆን፣ ከዚህ በመነሳት በፖለቲካ ስም በአገራችን ምድር የተካሄዱትን ስህተቶችና ወንጀሎች ለማሳየት ነው። በአጭሩ በአገራችን ምድር ሰፋና ጠለቅ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ ማለትም በፍልስፍና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በከተማ ግንባታ፣ በአርት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በኢኮኖሚክስና በሶስይሎጂ የሚደገፍና የሚገለጽ  ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለመዳበር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ስለማይታወቅም የዚህ አለመኖር ጉዳይ ጭንቅላታችን እንዳይብር ለማድረግ ችሏል የሚል ነው። የአውሮፓን የስልጣኔ ታሪክ የተመለከትክ እንደሆነ፣ የግሪክን ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስንና ማቲማትክስን መነሻ በማድረግ ነው በጊዜው የነበረውን ግትራዊ አስተሳሰብና ርስ በርስ መጨፋጨፍና ዲስፖቲያዊ አገዛዞችንም ሊቋቋሙና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ሊያስወግዱት የቻሉት። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ደግሞ በሳይንስና በፍልስፍና የተረጋገጠ ሲሆን፣ የሰውንም ልጅ ዕድገት ከአንትሮፖሎጂ አንጻር ስትመለከት ከፍራፍሬ ለቃሚ፣ እስከአዳኝና ከዚያ በኋላ እስከ ፊዩዳሊዝምና እስከ ካፒታሊዝም ድረስ እንዴት ለመጓዝ እንደቻለ እንረዳለን። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የግዴታና ኢቮሊሽናራዊ ጎዞ ሲሆን ለመሰረታዊ ለውጥ ግን የግዴታ ጭንቅላት በአርቆ አሳቢነት፣ በሎጂክና በዲያሌክቲካዊ የክርክር ዘዴዎች መኮትኮት አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ጭንቅላት ቀስ በቀስ የመዳበርና እያንዳንዱም ሰው ሰው መሆኑን ሊገነዘብ የሚችለውና በውስጥ የተደበቁ፣ እንደሞራል፣ እንደ ሰብአዊነት፣ ማዘንና መፀፀት፣ ፍቅር የመሳሰሉትና ጠቅላላውን የሰውን ልጅ ማክበርና ማፍቀር. ወዘተ. … ሊዳብሩ የሚችሉት። በሌላ ወገን ደግሞ በአውሮፓ ምድር ብቻ ካፒታሊዝም እንዴትና በምንስ ምክንያት እንዳደገና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ለመውሰድ እንደቻለ ለመረዳት የግዴታ የግሪክ ስልጣኔንና አስተዋፅዖውን መረዳት እንደሚያስፈልግ መሆኑን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ስለግሪክ ፍልስፍናና ሳይንስ ምርምር ሳይደረግ የኋላ ኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቅ ያለውንና የዳበረውን ፍልስፍናዊ ምርምርና የኋላ ኋላ ደግሞ በተፈጥሮ ሳይንስ ላይ የተደረገውን ርብርቦሽ መረዳት በፍጹም አይቻልም። ባጭሩ ለማሳየት የሞከርኩት የፈለገው ዐይነት አገዛዛና ሰው በአገራችን ምድር ስልጣንን ቢይዝ ከድህነት ለመላቀቅ እንደማንችል፣ ዕድሜያችንን በሙሉ በፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ እንደምንኳትን ለማሳየት ነው። በሌላ አነጋር፣ በምርጫ ብቻ አንድን ህብረተሰብና አገር መለወጥና ህዝቡንም የሳይ‹ንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ በፍጹም አይቻልም የሚል ነው። ስለሆነም ስለለውጥ በሚወራበት ጊዜ፣ ስለተቋማት የጥገና ለውጥ፣ ስለፖለቲካ የጥገና ለውጥ፣ ስለ ትምህርት ተቋማት መሻሻልና ችግርን በሚፈታ መልክ ማደራጀት፣ የውስጥ ገበያን ለማዳበር የግዴታ በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማትኮር፣ የሙያ ማስልጠኛ ቦታዎች በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋ ማድረግ፣ መንደሮችንና ከተማዎችን ለሰው እንዲስማሙ አድርጎ መገንባት፣ ትላልቅና ሰፋፊ መንገዶችን ከመስራት ይልቅ በመጀመሪያ ደረጃ በባቡር ሃዲድና በባቡር ግንባታ ላይ ማተኮር፣ ኮሎጆቾችና ዩኒቨርሲቲዎች የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ማዕከሎች ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ ማዘጋጀትና ወዘተ. … ስለለውጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና መረዳት ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ስለለውጥ በሚወራበት ጊዜ ሰፊው ህዝብ ሳይማር፣ ሳይነቃና ሳያውቅ፣ እንዲሁም ሳይደራጅ ስለለውጥ ማውራት በፍጹም አይቻልም። በአገራችንም ሆነ በአብዛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚሰራው ትልቁ ስህተትና ወንጀል ህዝብን ማዕክል ያላደረገና የማያሳትፍ ፖለቲካ የሚሉት ነገር ተግባራዊ ስለሚሆን ነው። ግልጽ እንዲሆንልህ፣ በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ከሌለ፣ የስፊው ህዝብ ጠበቃ ሊሆኑ የሚችሉ የሲቪል ሶሳይቲ ተቋማት እስከሌሉ ድረስና፣ ሰፊው ህዝብ የመንቃትና የመደራጀት መብት እስከሌለው ድረስ በየጊዜው አምባገነንና ፋሺሽታዊ ኃይሎች ስልጣንን በመጨበጥ የድህነትንና የጭቆናውን ዘመን ያራዝሙታል። እንደነዚህ ዐይነቶችን ፋሺስታዊና አምባገነናዊ አገዛዞችንም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሬ-ሀብትን የሚቀራመቱና አካባቢን የሚያወድሙና ለህብረተሰብ ውዝግብ ዋናው ምክንያት የሆኑ መልቲ-ናሽናል ኩባንያዎች  ይፈልጓቸዋል። እነዚህን ዐይነቶችን ዶንቆሮ የሆኑ ፋሺስታዊና አምባገነናዊ አገዛዞችን በመጠቀም ብቻ ነው ድህነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፋፉት። ስለሆነም ከህዝብ ንቃተ-ህሊናና ድርጃትዊ ስብስብ ውጭ የሚካሄድ ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ ፖለቲካዊ ውዝግብን መፍጠሩ የማይቀር ጉዳይ  ነው። በኢትዮጵያ ምድርም ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ የአገርን የጥሬ-ሀብትና የሰውን ጉልበትና ዕውቀት በስርዓት ለመጠቀምና የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማሟላት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ከተፈለገና ጠንካራ ማህበረሰም እንዲመሰረት ምኞታችንና ዋና ዓላማችን መሆን አለበት የምንል ከሆነ ሰፊው ህዝብ የግዴታ መማር፣ ማወቅና መንቃት እንዲሁም መደራጀቱ መታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም።

ከዚህ በመነሳት ነው የአቢይ አህመድን የአራት ዓመት ተኩል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምንነትና ተግባራዊነቱንም መመርመር የምንችለው። በአንተ አመለካከትና የመረጃ ጥናት መሰረት አቢይ ትልቅ ስራ ሰርቷል፤ አገራችንንም አንድ ዕርምጃ ወደፊት አራምዷል የሚል ነው። ይህ የአንተ ዕይታና ግንዛቤ ነው። ለዚህ ዐይነቱ ዕይታህና ግንዛቤህ የትኛውን ሳይንሳዊ ዘዴ እንደተከተልክ ለማወቅ በፍጹም አይቻልም። በተጨማሪም የተንሰራፋውን ድህነት ለመቅረፍ አቢይ የሚከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም ለማሳየት አልቻልክም። ዝምብለህ ብቻ በደፈናው አቢይ ይህንን ያንን አድርጓል እያልክና፣ እነዚህን እንደመረጃ በመውሰድ ነው ጽሁፌን ለመተቸት የምትቃጣው። ትችትህን ካነበብኩ በኋላ የምደርስበት ድምዳሜ ሳይንሳዊ ዕይታና መመሪያ፣ እንዲሁም የምትመራበት አንዳችም ርዕዮተ-ዓለም እንደሌለህ ነው።

ለማንኛውም ስለአንድ አገር ሁኔታ በሚወራበት ጊዜ ስለህዝቡና ስለአኗኗሩ ነው የሚወራው። ከዚህ በመቀጠልም ስለፖለቲካዊ አወቃቀር፣ ስለመንግስት መኪናና አገዛዙ ተግባራዊ ስለሚያደርገው ፖለቲካ፣ ይህም ማለት ጸጥታና ሰላምን ስለማስፈን ጉዳይ፣ እንደሚታወቀው ስላምና ጸጥታ በሌለበት አገር ውስጥ ምርትን በብዛትም ሆነ በጥራት ማምረት አይቻልም፤ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ግንባታ ወይም የውስጥ ገበያ ብለን የምንጠራውን መገንባትና ማዳበር በፍጽም አይቻልም። ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ሰፊው ህዝብም ራሱን ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ውስጥ ብቅ የሚሉ ፈጣሪዎች፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ሊወለዱና ለዕድገት አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ የሚችሉት። የሰላምና የፀጥታ መስፈን ደግሞ የቱን ያህል ለዕድገት አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር የታየና የተረጋገርጠ ጉዳይ ነው። እነዚህ አገሮች ባለፉት ሰባ አምስት ዐመታ የተሟላ ሰላም በማግኘታቸው ይኸው እንደምናየው በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ማህበረሰብ ለመመስረትና እኛንም ለማስተናገድ ችለዋል። በሌላ ወገን ደግሞ የእኛን ድንቁርና የተረዱት የአሜሪካና የአውሮፓ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የፀጥታ ኤሊቶች ጦርነትን ወደኛ አገር በማሸጋገር ርስ በራሳችን እንድንበላላ ለማድረግ በቅተዋል። ትርጉም በሌለውና እንደዚህ ብለህ ለመግለጽ በማትችለው መንገድ ርስ በራሳችን እየተሻኮትን ለብዙ ሚሊዮን ህዝብ ዕልቂት ምክንያት ለመሆን በቅተናል። በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ተማርን በሚሉት የሚቀሰቀስና ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በጥቅም በተገዙ ደንቆሮዎች ነው። ምስኪኑ ሰፊ ህዝብ እንደኛ የመሳሰለውን ደንቆሮ ኃይሎች ዝምብሎ ከመመልከትና እግዚአብሄርን ከመማፀን ውጭ የሚዋጋበት ምንም ዐይነት መሳሪያ የለውም።

ከዚህ ስንነሳ ዐቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ህዝብን ያሳተፈ፣ በህብረተሰባችን ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ማህበረሰብአዊ ቅራኔዎችን ሲፈታ አይታይም። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ተብሎ የሚገለጽና በቲዎሪ የሚተነተን የፖለቲካ ፍስልፍና ስለሌለው የሚካሂደው ፖለቲካ የሽወዳ ፖለቲካ ነው። የፖለቲካውን መድረክ ለፀረ-ህዝብና ለፀረ-ኢትዮጵያ፣ ለፀረ-ስልጣኔና ለፀረ-ዕድገት ኃይሎች ክፍት በማድረጉ ሰፊው ህዝብ በፍርሃት እንዲዋጥና አምላክን እየተማፀነ እንዲኖር አድርጎታል። በፖለቲካ ቲዎሪና ሳይንስ ውስጥ በፖለቲካና በነፃነት ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ዝምብሎ ማግበስበስ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ ዕውቀት ያላቸውን፣ የፖለቲካ ፍልስፍናቸው ምን እንደሆነና፣ ከዚህም በላይ ደግሞ በፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ላይ የጠራ አመለካከት ያላቸውንና ከዚህ ቀደምም በዚህ ዙሪያ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ህዝባዊና ብሄራዊ ባህርይ ያላቸውን ኃይሎች ብቻ በመሰብሰብና እንዲደራጁ ዕድል በመስጠት ብቻ ነው ጥልቀት ያለውንና የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር መፍታት የሚቻለው። አቢይ አህመድ እንደዚህ ከማድረግ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያላቸውንና፣ በሲአይኤና በአረብ ቱጃሮች የሚደገፉና ቱጃር ለመሆን የበቁ፣ በተለይም አንዳንድ ኦሮሞዎችን በመሰብሰብና አማካሪው በማድረግ ነው የፖለቲካውን መድረክ ያጨለመውና ዝብርቅርቁ እንዲወጣ ያደረገው። በእሱ አካባቢም ሆነ ከእሱ ውጭ የኦሮሞ ብሄረሰብን ጥቅም እናስጠብቃለን የሚሉትና በተሳሳተ ትረካ ወጣቱን የሚያሳስቱት በሙሉ በመሰረቱ በፖለቲካ መድረክ ዙሪያ መሰብሰብ የለባቸውም። እነዚህ ኃይሎች ስለፖለቲካም በፍጹም ማውራት የለባቸውም። እንደዚህ ስል ከአማራውና  ከሌሎች ብሄረሰቦች የተውጣጡ በፖለቲካ ስም የሚነግዱት የተሻለ የፖለቲካ ግንዛቤ አላቸው ለማለት አይደለም። ይኸው እንደምናየው በተለይም አማራውን እወክለዋለህ የሚለው ብአዴን የሚባለው ፍጡር ምንም ዐይነት ድርጅታዊ ቅርጽ የሌለው የአቢይ አቀንቃኛና ተጎታች ከመሆን ይልቅ ምንም የሚፈጽመው የሚጨበጥ ነገር የለም። የብአዴንን ሰዎች ስመለከት የቱን ያህል ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸውን ነው የምገነዘበው። በሎሌነት የሚያምኑና ምንም ዐይነት ትችታዊ አመለካከት(Critical Thought) ለማዳበር ያልቻሉ ናቸው።  ስለሆነም የአቢይ አህመድን ፖለቲካ ስንመለት የጌታና-የሎሌ ዐይነት ፖለቲካ የሚያራምድና፣ ካለምንም ትችትና አስተሳሰብ ዝምብላችሁ ተከተሉኝ የሚልና አሁን እንደምናየው ህግን በማስከበር ስም ወደ ማፊያነት የተለወጠ ነው። የዚህ ዐይነቱ የጌታና የሎሌ ፖለቲካ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድርና በአገራችንም የነበረ ሲሆን፣ የተገለጸላቸው የአውሮፓ ምሁራን እልክ አስጨራሽ ትግል በማካሄድ ነው ቀስ በቀስ የከበርቴው ዲሞክራሲ፣ ሪፓብሊካን አስተሳሰብና የህግ የበላይነት ተቀባይነት ሊያገኙ የቻሉት። ከዚህ ዐይነቱ የተገለጸለት አስተሳሰብ ስንነሳ ሌላው ቢቀር ከአፄ ኃይለስላሴ ፖለቲካ ጋር ስናወዳድረው የአቢይ አህመድ ፖለቲካ እጅግ ወደ ኋላ የቀረነአ ከፖለቲካ ቲዎሪ አንፃር ፖለቲካ የሚባል ስም ሊሰጠው የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ፖለቲካ በግለሰብአዊ ነፃነት የሚያምን፣ ህብረተሰብአዊ የሆነና የመንገስት ወይም የአንድ አገዛዝ ንብረት ያልሆነ ነገር ስለሆነ ነው። ከዚህም ባሻገር ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን በትችት መነጽርና ክርክር የሚዳብርና ህብረተሰብአዊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍቺያ መሳሪያ ነው። የአቢይ አህመድ ፖለቲካ እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦችና መመዘኛዎች የሚያሟላ አይደለም።

ይህንን መሰረት በማድረግ  የአራት ዓመት ተኩሉን የአቢይ አህመድን ፖለቲካ ስንመረመር ፖለቲካው ፖለቲካ ሳይሆን ሽወዳ የበዛበት፣ ውዝግብን ፈጣሪ የሆነ፣ ሰፊውን ህዝብ እፎይ ብሎ እንዳይኖር ያደረገ፣ ሰላምና ፀጥታ የጠፉበት ዘመን እንደሆነ እናያለን። ስለሆነም መረጃችን መመዘኛችን ህዝቡ የሚኖርበት ሁኔታና የሚዳሰስውና በረቀቀ መልክ የሚታየው ጉዳይ ነው። አቢይና ግብረአበሮቹ፣ እንዲሁም በጠቅላላው በአገዛዙ ውስጥ የተካተቱት ኃይሎች በሙሉ ሰፋ ያለና በሳይንስ የተፈተነ ዕውቀት ስለሌላቸውና በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥም ያላለፉ በመሆናቸው ህብረተሰቡን ከመበወዝና ስቃይ ከማሳየት ውጭ ሌላ የሚሰሩት ነገር በፍጹም የለም። ይህ ዐይነቱ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ  ጽንፈኝነትንና የተሳሳተ ትረካን ያስፋፋ ነው።  በመሆኑም አቢይ ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ ነው ሰው በማንነቱ የሚገደለው፤ ወጣቶች የሚሳደዱት፤ ቤተክርስቲያናት የሚቃጠሉትና ምዕመናን የሚሳደዱት። እንዲሁም አንድን መንደርና ከተማ ያቀናና የገነባ መጤ እየተባለ የሚፈናቀለውና የሚገደለው በዚህ በአቢይ አህመድ የአራት ዓመት ተኩል የአገዛዝ ዘመን ነው። አቢይ ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ ነው በአገራችን ምድር የውስጥ ስደተኝነት የተስፋፋውና ሰፊው ህዝብም በመጠለያ ቦታዎች እንዲኖር የተገደደው። እንደ ሻሸመኔና አልጣዬ የመሳሰሉት ከተማዎች የወደሙት በአምላክ ፈቃድ ከላይ ሳይሆን በአቢይ ዘመን በመንግስት በተደገፈ ኦነግ ሸኔ በሚባል ኃይል ነው። በተለይም አቢይ የጴንጤ ቆንጤ ኃይማኖት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን በአገራችን ታሪክ፣ ባህልና በሃይማኖቱ ላይ “የመስቀል ጦርነት “ ነው ያወጀው። ስለሆነም አንተ በማስረጃ የተደገፈ አቀራረብ አይደለም ብለህ ጽሁፌን ስትተች ለማየት ያልቻለከው በምድር ላይ ያለውንና ህዝባችንን የሚኖርበትን የኖሮ ሁኔታ ነው። አንተ በአቢይ ፍቅር የተጠመድክ ስለሆነክ በህዝባችን ላይ የሚደርሱት አደጋዎች፣ ማለትም መገደል፣ መፈናቀል፣ መራብ፣ በአንድ አካባቢ የአገር ውስጥ ስደተኛ ሆኖ መታጎር፣ እነዚህና ለሰው ጭንቅላት የሚዘገንኑ ነገሮች በሙሉ አይታዩህም። በዕውነተኛ ሳይንስ ምርምር መረጃ የሚባለው ነገር  እንደማስረጃ ወይም መለኪያ ሆኖም ሊወሰድ የሚችለው ሰፊው ህዝብ የሚኖርበትን ሁኔታ በማየትና በመርመር ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ የምርምር ዘዴ ኖርማቲቭ ሳይንስ ይባላል። መሆን አለበት ከሚለው በመነሳት በዐይን የሚታዩና የማይታዩ ነገሮችን በመመርመር ጤናማ መልክ እንዲኖራቸው ማድረግና ለዚህም አጥብቆ መታገል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አንተ ሳታውቀው የምትመራበት ሳይንስ ፖዘቲቭ ሳይንስ ይባላል። ይህም ማለት አንዳንድ ለውጥ የሚመስሉ አሰመሳይ ነገሮችን፣ ወይም ደግሞ አንዳንድ ተናጠል ነገሮችን በመውሰድና ጥቂቶችን የሚማርኩ ነገሮችን ተግባራዊ በማድረግ ይህ ነው ለውጥ በማለት እነዚህን እንደማስረጃ ለመወሰድ ትሞክራለህ። ይህንን ዐይነት የተናጠል ሳይንሳዊ የምርመራ ዘዴ፣ በመሰረቱ ፀረ-ሳይንሳዊ ዘዴ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለው የሚመራበትና አብዛኛዎችን የሶስተኛው ዓለም ኤሊቶችን የሚያሳስትበት ዘዴ ነው።  ለማንኛውም ፓርክ ቢሰራና ወታደር በአዲስ መልክ ቢዋቀር ይህ በራሱ እንደ መረጃ ሊቆጠር በፍጹም አይችልም። አንድ ህዝብ የሚፈልገው ሰላምንና ጸጥታን፣ እንዲሁም ደግሞ በልቶ ማደርንና መጠለያን እንደመሆኑ መጠን እንደመረጃ መወሰድ ያለበት ጉዳይ በአራት ዓመት ተኩል ውስጥ ህዝቡ በኑሮው ተሻሽሏል ወይ? ድህነት ተቀርፏል ወይ? ወጣቱ የሙያ ትምህርት ዕድል አግኝቷል ወይ? የመጠለያ ጉዳይ መስመር ይዟል ወይ?  ወዘተ. … በማለት እንጂ በደንብ ያልሰለጠነ ወታደርና ምሁራዊ ብቃት የሌለውን በማሳየት የተቋማት ለውጥ እንደትካሄደ አድርጎና ይህንን እንደማስረጃ መቁጠር የቱን ያህል የተዛባ አመለካከት እንዳለህ ነው የሚያረጋግጠው።

የአራት ዐመትን ተኩሉን የአቢይ አህመድ ፖለቲካ በደንብ እንዲገባህ እንደሚከተለው ለማስፈር እሞክራለሁ። በዛሬው ምድር በአገራችን ምድር የህግ የበላይነትን የሚጻረር አገዛዝ በአገራችን ምድር ሰፍኗል ማለት ይቻላል። እንደምታወቀው በአገራችን ምድር ይይስሙላ ያህል ምርጫ ተካሂዷል። የምርጫውንም ሂደት ለተከታተለ አንድ በብልጽግና ስም የሚያወናብድ ድርጅት ራሱ ተወዳድሮ ራሱ ብቻ በአሸናፊነት ወጣሁ ያለበት ሁኔታን እንመለከታለን። ስለሆነም ከ95% በላይ የሚሆነው የህዝብ ተወካኝ ነኝ የሚለውና በፓርሊያሜንት ውስጥ የተቀመጠው የአንድ ፓርቲ አባል ብቻ ነው። በዚህ ዐይነት ፓርሊያሜንት ውስጥ በፍራክሽን ደረጃ ራሳቸው ተዋቅረው የገአዛዙን ፖሊሲ ሊቃወሙና አማራጭም ሊያቀርቡ የሚችሉ ሌሎች ፓርቲዎች የሉም ማለት ነው። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የአገዛዙን ፖሊሲ ለመመርምር የሚችሉ የፓርሊያሜንታሪ አጣሪ ኮሚቲዎች ማቋቋም በፍጹም አይቻልም። የፓርሊያሜንታሪ አጣሪ ኮሚቴ በሌለበትና፣ እያንዳንዱ ሚኒስተር ተጠያቂ ሊሆን በማይችልበት ፓርሊያሜንትና የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ ደግሞ  አንድ ግለሰብ እንደፈለገው ሊያደርግ ይችላል ማለት ነው። ባጭሩ የአገራችንን የፖለቲካ አወቃቀር ሁኔታ ስናይ በሶስቱም የአገዛዝ መዋቅሮች፣ በኤክስኩቲቭ፣ በሌጂስለቲቭና በዪዲካቲቭ መሀከል መንም ዐይነት የስራ ክፍፍል የለም። ኤክስኩቲቩም በፓርሊያሜንቱ ቁጥጥር የሚደረግብት ሳይሆን አቢይ እንደፈለገው የሚጫወትባትና ከሳይንስና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ውጭ እንደፈለገው የሚዘላብድበት መድረክ ለመሆን በቅቷል። አቢይ ፓርሊያሜንት ፊት ቀርቦ የሚሰጠው ማብራሪያ በጽሁፍ በደንብ ያልተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን በሚገባ ለመክታተል የሚያስቸግር ነው። ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ሚኒስተር በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ፓርሊያሜንት ፊት በመቆም ምን ምን ነገሮችን እንደሰራና፣ ወደፊትስ ምን ምን ነገሮች እንደሚሰሩ ገለጻ ማድረግ አለበት። ዕውነተኛው የፓርሊያሜንታሪ የአሰራር ዘዴ ይህ ሲሆን አንድ ግለሰብ ብቻ “ሌክችር” የሚሰጥበት ሁኔታ በፍጹም መፈጠር የለበትም።

ከዚህ አጠቃላይና አጭር ሀተታ ስንነሳ በአገራችን ምድር ፈሺሽታዊ ወይም አምባገነናዊ አገዛዝ ሰፍኗል ማለት ይቻላል። ፍርድቤትና ዳኞች፣ እንዲሁም አቃቢ ህግ ቦታ የሌላቸው ናቸው። ከላይ በመጣ ትዕዛዝ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋች የሆኑ ግለሰቦች ህግን ለማስከበር በሚል ስም የሚታፈኑበት ሁኔታ በአገራችን ምድር ሰፍናል ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር ፖሊሱንና ፀጥታውን የሚቆጣጠርና የሚያዝ ማፊያዊ አገዛዝ ሰፍኗል ማለት ይቻላል።  በዚህ መልክ የፖለቲካ ነፃነት በፍጹም የለም፤ አገዛዙ የሚወስደውን የአገርን ህልውናና የህዝብን ደህንነት የሚፃረር ፖለቲካ የሚባለውን ነገር መተቸት አይቻልም። አቢይ እንደሚለን በፍጹም አትተቹኝ ነው። ያልገባው ነገር አንድ አገዛዝ  ወይም ግለሰብ አምላክ ሳይሆን የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑና ህዝብንም እወክላለሁ ወይም አስተዳድራለሁ እስካለ ድረስ ስራው ሁሉ በሳይንስ መመርመርና መመዘን፣ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ መተቸት ያለበት ጉዳይ ነው። በፖለቲካ ሳይንስና በሌሎችም የሳይንስ ዘርፍ ትችት መሰረታዊና ለፈጠራም የሚያመች ነው። ትችት በሌለበት አገር ጤናማና የተስተካከለ ዕድገት በፍጹም ሊኖር አይችልም። ስለሆነም አትተቹኝ ማለት እኔው ነኝ ፈላጭና ቆራጭ፣ የማጎርስህን መጥፎ ነገርም ቢሆን ዝምብለህ ጉረስ እንደማለት ነው። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ኃላፊ ወይም ሟች እንደመሆኑ መጠን አንድን ህዝብ የሚመለከት ነገር ሁሉ ተከታታይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ሳይንሳዊ ምርምርና ትችት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ።

የፖለቲውን ሁኔታ ትተን ወደ አገዛዙ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመጣ አቢይና የኢኮኖሚ ሚኒስተሩ በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲና የኢኮኖሚ ቲዎሪ እንደሚመሩና የአገራችንን ኢኮኖሚ በተሟላ መንገድ ለመገንባት እንደሚችሉ ግልጽ የሆነላቸው አይመስለኝም። በተለያየ ጽሁፌ ለማሳየት እንደሞከርኩት የወያኔ አገዛዝ 27 ዐመታት ያህል ተግባራዊ ያደረገው የእኮኖሚ ፖሊሲ ኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወይም የመዋቅር ማስተካከያ (Structural Adjustment Programs) እየተባለ የሚጠራው በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በእነ ዓለም ባንክ የተደነገገና አብዛኛዎችን የሶስተኛው ዓለም አገሮች በድህነት ውስጥ እንዲማቅቁ ያደረገና፣ በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ የካፒታሊዝም ግንባታ ታሪክና ሂደት ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ የማያውቅ ኢ-ሳይንሳዊ ፖሊሲ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አቢይ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በወያኔ ዘመን ተግባራዊ የሆነው ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምን ድህነትን ፈልፋይ ሊሆን ቻለ? ለምንስ ጥቂቱ ሀብታም ሊሆን በቃ? የጥገና ለውጥን ስም የያዘው የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምንስ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት መሰረት አልጣለም? በየጊዜው እያደገ ለመጣው የዋጋ ግሽበትስ ዋናው ምክንያት ምንድነው? ለምንስ የሰፊው ህዝብ የመግዛት ኃይል ሊያድግ አልቻልም? ለምንስ ስራ ለሚፈልገው በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠረው ህዝብ የስራ መስክ ለመፍጠር አልተቻለም? እያለ ጥናት አልተካሄደም። የአቢይ አገዛዝ የወያኔ አገዛዝ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም ስላልገባው በዚያው የድህነትን ፈልፋይ ፖሊሲ ነው የቀጠለው። እንድምናየው በሊበራላያዜሽን ስም ህዝቡን እያወናበደ ነው። የባንኩንም ዘርፍ ሊበራላይዝ መሆን አለበት እየተባለ ይወተወታል። እነዚህ ሊበራላይዝድ ወይም ከመንግስት ቁጥጥር ስር መውጣት አለባቸው የሚባሉት የኢኮኖሚ መስኮች ደግሞ ፈጠራ የሚካሄድባቸውና ምርት የሚመረትባቸው ዘርፎች አይደሉም። ስለኢኮኖሚ የጥገና ለውጥም በምናወራበት ጊዜ ከምርት፣ ከሳይንስ ከቴክኖሎጂ፣ ከትናንሽና ከማዕከለኛው ኢንዱስትሪዎች መቋቋም አንፃር ብቻ ማየትና መነሳት ያለብን እንጂ አገልግሎት መስጫ(Service Sector) ድርጅቶችን ወይም ኩባንያዎችን ሊበራላይዝ በማድረግ ምንም ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገትና መሰረታዊ ለውጥ በፍጹም ሊመጣ አይችልም። ማንኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ ወይም የግልጋሎት መስጫዎች በሙሉ በምርት ክንዋኔ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ የሚመኩ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ምርት በጥራትም ሆነ በብዛት በማይመረትበት አገር የአገልግሎት መስክና ሊበራልይዝ በማድረግ የሚገኝ ምንም ፋይዳ የለም። ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው መሰረት እስካልሆነ ድረስ በአገልግሎት መስክ አንድ አገር በተሟላ መልክ ልታድግ አትችልም። የባንኩ ዘርፍ ከምርት ማምራቻ፣ ወይም ከሚታዩ፣ ከመጨበጡና ከሚዳሰሱ ነገሮች ጋር እስካልተያያዘ ድረስ በራሱ ወደ ግልሀብትነት መለወጡ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የባንክም ትርጉም ወይም ደግሞ የፋይናንስ ትርጉም በመሰረቱ ገንዝበ ለምርታማ ነገሮች በመዋዕለ-ነዋይ ስም እንዲፈስ በማድረግ በገንዘብና በምርት ክንውን፣ እንዲሁም ከሳንይስና ከቴክኖሎጂ ጋር በማያያዝ ሚዛናዊ የሆነ ዕድገት እንዲመጣ ለማድረግ ነው። ዛሬ በአገራችን ምድር ያለው ትልቁ ችግር፣ በተለይም ህዝቡ የሚማረርበት የዋጋ መናር ጉዳይ ዋናው ምክንያት አብዛኛው ገንዘብ በአገልግሎት መስኩ ጋ ስለሚፈስና በዚህ ውስጥ ስለሚሽከረከርና ከምርት፣ ከምርምርና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ለመያያዝ ባለመቻሉ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የሚያረጋግጠው በአገራችን ምድር የኢኮኖሚ ቲዎሪንና ፖሊሲን፣ እንዲሁም የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ጉዳይ በተመለከተ ከፍተኛ የግንዛቤ እጦት እንዳለ ነው። የገንዘብ ጥንካሬ መኖርና አለመኖር፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ሰፋ ባለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮችም ርስ በራሳቸው እስካልተሳሰሩ ድረስና ገንዝብም በፍጥነት ከአንደኛው መስክ ወደ ሌላኛው መስክ የመተላለፍ ዕድል እስካላገኘ ድረስና፣ የሰፊው ህዝብም የመግዛት ኃይል በየጊዜው የማይጨምር እስከሆነ ድረስ ገንዘብ ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሆን ውስጣዊ ጥንካሬ ለማግኘት አይችልም። በሌላ አነጋገር የአንድ አገር የገንዘብ ጥንካሬ የሚለካው በጠንካራ የምርት መሰረት፣ በአገር ውስጥ ገበያ መዳበር፣ የኢኮኖሚው ዘርፎች ርስ በርስ መያያዝና መደጋገፍ፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት በሚንቀሳቀስና በሚደገፍ የምርት ክንውን ብቻ ነው። ከዚህም ባሻገር ብቃትነትና ሰፊውን ህዝብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊያዘዋውሩ የሚችሉ እንደባቡር ሃዲድና፣ የምሬት ውስጥ ባቡርና የትራም ስይስተም ለኢኮኖሚው ዕድገትና ለገንዘብ ጥንካሬ ዕምርታን ይሰጡታል፤ የጀርባም አጥንቶች ናቸው። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ አተናተንና በተግባርም ከተረጋገጠው ሁኔታ ስንነሳ የአቢይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አገር አፍራሽና ድህነትን ፈልፋይ ከሆነው የወያኔው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ፖሊስ በፍጹም ያልተላቀቀ ነው። በአጭሩ በአገራችን ምድር ሳይንሳዊ የሆነና በፍልስፍና የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ያለው።

ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አለመኖርና ተግባራዊ አለመሆን ደግሞ ማህበራዊ መዛባት ይፈጠራል። ድህነት ይፈለፈላል። ሁሉም ነገር በተዝረከረከ መልክ እንዲሰራ ይሆናል። የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል ከአለአግባብ እንዲባክኑ ይደረጋሉ። አቅድ የሌላቸው የቤት አሰራሮች ይሰራሉ። አካባቢ ይቆሽሻል። ከውጭ በሚመጡ ለሰው ልጅ በማይጠቅሙ ቁሳቁሳዊ ነገሮች የተነሳ አካባቢ ከመቆሸሹና ተፈጥሮም ከመመረዙም ባሻገር የሰው ልጅ ጤንነት ይቃወሳል። መንፈሱም ይረበሻል። በ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመኑ ወያኔ ጥሎልን የሄደው ግፍ ይህንን ነው የሚመስለው። በሁሉም አቅጣጫ የተዛባች ኢትዮጵያን!! በመሆኑም አቢይን ይህንን ዐይነቱን አካባቢን የሚያወድም፣ ተፈጥሮን የሚያስበዘብዝ፣ ለውጭ በዝባዢዎች ክፍት የሚያደርግና ህዝባችንን ለዝንተ-ዓለም በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲማቅቅ የሚያደርግ በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ የተደገፈ ሳይንሳዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ  በመከተልና ተግባራዊ በማድረግ ነው የአገራችንን ኋላ-ቀርነት ጥልቀት የሚሰጠውና ህዝባችን፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱ ተስፋው እንዲጨልም የሚያደርገው።

ስለሆነም ትግላችንናና የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወያኔ ተግባራዊ ካደረገው ባሸገርና፣ በአገራችን ምድር ሰላምን የሚያስፍን፣ ግለሰብአዊ ነፃነትን የሚያስከብር፤ አገዛዙና መንግስት የሚባሉት ፍጡሮች የህግ የበላይነትን የሚያከብሩበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብ አገልጋይ መሆናቸውን የሚረዱበት ሁኔታ ነው መሆን ያለበት። ከጎጠኝነትና ከጽንፈኝነት ይልቅ ዕውነተኛ የሪፓብሊካን አስተሳሰብ የሚተገበርበት አገር ነው የምንመኘውና የምንታገለው። የመጨረሻ መጨረሻ ትግላችንና ዋናው ዓላማችን የተከበረች፣ የማትደፈር፣ ህዝባችን እፎይ ብሎ የሚኖርባትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ከዚህ መመዘኛችን ስንነሳ አቢይና አገዛዙ አንዳቸውንም መመዘኛ የሚያሟሉ አይደሉም። አገሪቱን ወደጦር አውድማነት በመለወጥ ብሄራዊ ነፃነታችን እንዲደፈር ያደረገ ነው። ግብጽና ሱዳን እንዲወሩን ሁኔታውን በሙሉ አመቻችቷል። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደፈለገው ለወያኔ መሳሪያ እንዲያቀብልና አማራውንና የአፋሩን ወገናችንን እንዲወጋ ሁኒታውን በሙሉ አመቻችቷል። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥና ስንትና ስንት ወንጀል ከሰራ ኃይል ጋር አቢይ የዕርቅ ድርድር ለማድረግ ደፋ ቀና ሲል እንመለከታለን። በዚያው መጠንም ህዝባችንን ለሚወጋውና አገራችንን ለማፈራስረስ ለሚሯሯጠው  ወያኔ የ40 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድብሎታል። ምግብና መድሃኒት በሺሆች መኪናዎች በመጫን ወደ ትግሬ ይጓዛሉ። በአጭሩ  እኛ እየቀለብንህ ውጋን፤ አገራችንንም ማውደም ትችላለህ እያለ ነው አቢይና አገዛዙ በአገራችንና ህዝባችን ላይ የታሪክ ወንጀል የሚፈጽመውና የሚቀልደው። በአንጻሩ አማራው በማንነቱ እየተፈናቀለና እየተሰደደ ርዳታ እንዳያገኝ የተደረገበትን ሁኔታ እንመለከታለን። መጠለያ ባገኘባቸው አካባቢዎች ደግሞ የተቀነባበረና በአካባቢው አስተዳደርና በፌዴራል አገዛዙ ምንም ዐይነት ዕርዳታ አይደረግለትም። ቂም-በቀል ለመወጣት በሚልና፣ ከርጅም ጊዜ አንፃር በአሜሪካኖችና በአውሮፓ አንድነት ግፊት ወልቃይት-ጠገዴን ለወያኔ ለመስጠት በማሰብ አካባቢውን ለማስተዳደር የሚያስችል በጀት አልተመደበም። የአሜሪካኖችም ዋና ዓላማ ወልቃይት-ጠገዴን ለወያኔ በማስረከብ የመልቲ- ናሽናል ኩባንያዎቻቸውን በማስፈርና ተትረፍርፎ የሚገኘውን ወርቅና ልዩ ልዩ የጥሬና የእርሻ ሀብቶች በመዝረፍና ወደ አሜሪካ በማስተላልፍ የካፒታሊዝምን መደለብ ለማፋጠን ነው። በዚህ ዐይነቱ አካሄድ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ  ማንኛውንም አሻጥር እየሰሩና ምስኪኑን ህዝብ እያሰቃዩት ለመሆኑ ሁኔታው ያረጋግጣል።

ከዚህ ስንነሳ አቢይ አህመድ ብሄራዊ ባህርይ የሌለው ነው። ይህም ማለት የታሪክ ንቃተ-ህሊና፣ የባህል ንቃተ-ህሊና፣ የተፈጥሮ ንቃተ-ህሊና የጎደለውና አገርና ህዝብ ምን እንደሆኑ ያልገባው ነው። ስለብሄራዊ የኢኖሚ ምንነትም የተረዳ ባለመሆኑና አገራችንን ወደ ተበዝባዥነት ለመለወጥ ሽር ጉድ የሚል በመሆኑ ብሄራዊና አገር-ወዳድ ባህርይ የለውም። በአንዳች ሰይጣናዊ ኃይል ይመራ ይመስል አገራችንን ለማውደም እየተቅበዘበዘ ነው። ስራው ሁሉ የሚገርምና የሚያበሽቅም ነው። በማንኛውም የሳይንስና የፍልስፍና መለኪያ ሊመዘን የማይችል ነው። ስለሆነም በእኔና በአንተ መሀከል የሰማይና የመሬትን ያህል ልዩነት አለ። አንተ ከፀረ-ዲሞክራሲ አንፃር ስትነሳና አንድን ግለሰብ ስታወድስና እንደ አምላክም ስትቆጥር ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ሳይንስን የሚቀናቀንና ያረጀና የአስራ አምስተኛው ክፍለ.-ዘመን አስተሳሰብ ነው እልሃለሁ። ባጭሩ የትግል ስልታችን፣ የመርመሪያ ዘዴያችን፣ ነገሮችን የምንመለከትበት መነጽርና ፍርድ የምንሰጥበት መለኪያ የሰማይና የመሬትን ያህል የሚራራቅ ነው ማለት ነው። አንተ ህዝብን ስትንቅና ብሄራዊ ነፃነትችን የሚያስደፍርና ጦርነትን ቀስቃሽ´ ግለሰብ ስታመልክ እኔ ደግሞ ህዝብን የማከብርና አገሬን የምወድ ነኝ።  በተረፈ ለትችትህ በጣም አመሰግንሃለህ። መልካም ግንዛቤ!!

                                                                            fekadubekele@gmx.de