[gtranslate]

    ፖለቲከኛ ነን ባዮች በፖለቲካ ስም የሚሰሩት ትልቅ የታሪክ ወንጀል-ክፍል አምስት

                                                                 ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

                                                       ህዳር 25 2020

መግቢያ

እ.ኢ.አ በ24.2.2013 እኩለ ሌሊት ላይ አረመኔውና ፋሺሽቱ የህውሃት ቡድን በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ ወታደር ላይ ምንም ሳይታሰብ ጨለማን ተገን በማድረግ አረመኔያዊ ድርጊት መፈጸሙ በታሪክ ውስጥ ተሰምቶም ታይቶም በፍጹም አይታወቅም። ስንትና ስንት ዐመታት አብረው በኖሩ፣ ሃሳብ ለሃሳብ በተጋሩና ወንድሞቻችን ናቸው ብለው ሙሉ ዕምነት በጣሉባቸው፣ ከተለያዩ ክልል የመጡና በተለይም ከአማራው ብሄረሰብ በተውጣጡ የአገራችን ወታደሮች ላይ  በህውሃት ካድሬዎች  የተከፈተው ጦርነትና በወንድሞቻችንም ላይ የደረሰው ዕልቂት በጣም የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ነው። እንደሚባለው ከሆነ መለስተኛና ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው ከስድስት መቶ በላይ የሚቆጠሩ አገር ወዳድና ግዴታቸውን የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ህይወታቸው እንዲቀጥፍ ተደርጓል። ፋሺሽቱ የህውሃት አመራር በወታደሩ ውስጥ በተሰገሰጉ ካድሬዎቹ እንደዚህ ዐይነቱን ፋሺሽታዊ ዕልቂት እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ሲሰጥ ዋናው ዓላማው የሰሜኑን ዕዝ ጦር በመቆጣጠርና መሳሪያዎችን በመንጠቅ በቀላሉ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ እንደገና ስልጣን ላይ በመውጣት ሌላ የፋሺሽታዊ አገዛዝ መዋቅሩን በመዘርጋት ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ጠቅላላውን የኢትዮጵያን ግዛት በመቆጣጠር የጨለማና የድህነት ዘመኑን ለማራዘም ነበር። ይሁንና ግን ይህ እርኩስና ፋሺሽታዊ ድርጊቱና ህልሙ ቆራጥ በሆኑ አገር ወዳድ መኮንኖችና ወታደሮች በስንት መስዋዕትነት ሊከሽፍ በቅቷል። ይኸው ሰሞኑን እንደምንከታተለው የህውሃት ወታደር በታከታታይ ሽንፈት እየደረሰበትና ያሰለጠናቸውም ወታደሮች ወይም የክልሉ ኃይሎችና ሚሊሺያኖች የተቀሩት በጦር ሜዳ ሲሰው፣ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል እየሸሹና አንዳንዶቹም ደግሞ እጃቸውን እየሰጡ ነው።

ይህ ህወሃት የጀመረው ጦርነትና ያደረሰው ዕልቂት በጣም የሚያሳዝንና የሚያስቆጭም ቢሆን በአንዳንድ ተንታኞች ዕምነት ይህ የህውሃት ድርጊት የእግዚአብሄር ስጦታ ነው ብለው የሚተረጉሙ አሉ። ሁላችንም እንደምናውቀው በአገራችን ምድር ለውጥ መጥቷል ከተባለ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ጀምሮ ህውሃት እንደገና ስልጣን ላይ ለመውጣት ሲል ያልሞከረው ነገርና ያልከፈተው ጦርነት የለም። በተለይም ኦነግ ሸኔ ከሚባለው ፋሺሽታዊ አሸባሪ ቡድንና ከእነጀዋርና ሌሎች ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በማበር፣ በገንዘብ በመደገፍና መሳሪያ በማስታጠቅ በተለይም በምዕራብ ወለጋና በቤኒሻጉል ክልል ጦርነት በመክፈት በተለይም በከፍተኛ ደረጃ በሚጠላው የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ጦርነት በመክፈት ብዙ ዕልቂት አድርሷል; ብዙ ንብረትም አውድሟል። ፋሺሽቱ የህውሃት ቡድን በዚህ ዐይነት የሽብር ተግባር ሲሰማራና ሌሎችንም ሲያስታጥቅ የአጭር ጊዜ አላማው ስልጣን ላይ ተመልሶ መምጣት ቢሆንም፣ የረጅም ጊዜ አላማው ደግሞ አገሪቱን ወደ ዘለዓለማዊ ወይም በቀላሉ መቋጠሪያ የማያገኝ ጦርነት ውስጥ በመክተት የኢትዮጵያን ህዝብ ሰቆቃ ማርዘመና የዘመናዊነቱን ወይም የስልጣኔውን መንገድ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መዝጋት ነው።

ይህንን ህወሃት የከፈተውንና በወድንሞቻችን ላይ ያደረሰውን አረመኔያዊነት የተሞላበትን ድርጊት አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ነን ባዮች ጦርነቱ በወንድማማቾች መሀከል የሚካሄድ አድርገው በማቅረብ የህውሃትን ፋሺሽታዊ ድርጊት አቃለው በማሳየት ብዙ የዋህ ሰዎችን በማሳሳት ላይ ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ ግለሰቦችና ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ የሚመስሉ ድርጅቶች ህውሃት ስልጣን ይዞ 27 ዓመት ያህል አገራችንን ሲገዛ የፈጸመውን ወንጀል  አይ በደንብ አላጤኑም፣ አሊያም ደግሞ ትክክል ነው ብለው ተቀብለዋል ማለት ነው። ህውሃት 27 ዓመታት ያህል አገራችንን ሲገዛ አገሪቱን በብሄረሰብ በመሽንሸንና አርቲፊሻል የማንነት ሁኔታን ሲፈጥር ዋና ዓላማው እያንዳንዱ ብሄረሰብ ነፃ እንዲወጣና የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማድረግ ሳይሆን በየክልሉ የጎብዝ አለቆች(War Lords) አገዛዝ በመፍጠር የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲን በማጠናከር ዘረፋ ጥሬ-ሀብትንና ምግብ ነክ ነገሮችን በመዝረፍ፣ በዚህም አማካይነት ትግራይን በኢንድሱትሪ ማበልጸግ ነው። ከዚህም በላይ በዚህ አማካይነት የኢምፔሪያሊስቶችን ተልዕኮ በማሟላት ህዝባችን እርስ በእርሱ እየተናከሰ እንዲኖር ለማድረግና አቅጣጫው ሁሉ እንዲጨልምበት ለማድረግ ነው። ስለሆነም ወያኔ የቀሰቀሰው ጦርነትና በጀግኖች ወታደሮቻችን ላይ ያደረሰው ዕልቂት በወንድማማቾች መሀከል እንደሚካሄድ ዐይነት ጦርነት ሊተረጎም የሚገባው አይደለም። የኢትዮጵያ ወታደር በስልትና በተቀናጀ ሁኔታ የሚያካሂደው ጦርነት በትግራይ ብሄረሰብ ላይ ወይም በእህቶቻችንና በወንድሞቻችን ላይ የተቃጣ ሳይሆን በወንበዴውና በፋሺሽቱ የወያኔ ኃይልና አመራሩ ላይ ብቻ ነው። ይህም ዕርምጃ ፍትሃዊና ወታደሩም የትግራይን ክልል ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከህውሃትና ከካድሬዎቹ መዳፍ  ስር በማላቀቅ ህዝቡ በነፃነት የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ በመፍጠር፣ በዚያ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በአገሪቱ ምድር አስተማማኝና ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር ነው። በዚህ ዐይነቱ የጀግንነት ድርጊት ማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ከወታደሩ ጎን መሰለፍና የተቻለውን ድጋፍ ማድረግ አለበት። በሌላ ወገን ግን ደብረ-ጽዮንና ቡድኑ ኃይላቸው እየደካመና መግቢያ መውጫ እያጡ ሲመጡ ከጦርነት ይልቅ በድርድር እንፍታው በማለት ለአፍሪካ አንድነትና ለምዕራብ መንግስታትም ኤምባሲዎች ደብዳቤዎች በመጻፍ ጦርኑቱን ዓለማዊ ትርጉም ለመስጠትና ጊዜ ለማግኝት ሲጥሩ ይታያል። በመቅጽበት ከስድስት መቶ በላይ የሚገመት ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው መኮንኖችና ወታደሮች ከገደሉና በተጨማሪም ምንም ባልታጠቀ ህዝብ ላይ አማራ በመሆኑ ብቻ አሰቃቂ ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ ችግራችንን በድርድር እንፍታው ማለት የቱን ያህል ጭንቅላታቸው እንደማይሰራ ነው የሚያረጋግጠው። በተለይም የአገራችን መከላክያ ድል በድል ከሆነና ብዙ ቦታችዎችን በመቆጣጠር ላይ በሚገኝበት ወቅት እንደዚህ ዐይነቱ ነገር እንደማይታሰብ ግልጽ በሆነላቸው ነበር።  ከዚህ ስንነሳ ጦርነቱን ተራ የስልጣን ጦርነትና በዶ/ር አቢይና በህውሃቶች መሀከል የሚደረግ ጦርነት ነው ብሎ መተርጎም በጣም አደገኛ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከህውሃት ጎን እንደመቆም ይቆጠራል።

ከዚህ ባሻገር አንዳንዶች ይህንን ጦርነት ፖለቲካዊ ትርጉም ለመስጠት የሞከሩና የሚሞክሩ አሉ።  ለውጥ መጣ ከተባለ ጀምሮና ከዚያም በፊትም ህውሃት የሚባለው ፋሺሽታዊ ቡድን ስለፖለቲካ ያለው ግንዛቤ አልቦ ነው ማለት ይችላላ። 27 ዓመት በሙሉ አገራችንና ህዝባችንን ረግጦ ሲገዛ በፖለቲካ ዘይቤ ወይም በአንዳች የፖለቲካ ፍልስፍና በመመራት ሳይሆን የውንብድናን አገዛዝና ሸፍጠኝነትን በማስፋፋት ነው። እንደሚታወቀው በ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመኑ ህዝባችን የመደራጀትና ሃሳቡን በይፋ የመግለጽና ሰላማዊ ሰልፍም የማድረግ መብት አልነበረውም። ያደርግ የነበረው ፀረ-ስልጣኔ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማካሄድ የተወሰነውን ህብረተሰብ በማባለግ የባህል ውድቀት ማስከተል ነበር። ስለሆነም በትግራይ ክልል በፋሺሽቱ የወያኔ ኃይልና በኢትዮጵያ ወታደር መሀከል የሚካሄደው ጦርነት በመደራደር ወይም በፖለቲካ የሚፈታ ሳይሆን በጦርነት ብቻ ነው።  በተለይም ወታደራችን ድል በድል እየተቀዳጀ ወደ ፊት በሚራመድበት ጊዜና ስትራቴጂክ ከተማዎችንና ቦታዎችን ነፃ በሚያወጣበትና በሚቆጣጠርበት ጊዜ ችግሩን ከጦርነት ይልቅ ያለውን ውዝግብ በድርድር ወይም በፖለቲካ ውይይት መፍታት ነው የሚለው አላዋቂነትና ትጥቅ እንደማስፈታት ይቆጠራል። ከዚህ ስንነሳ የወያኔን ድርጊት በመደገፍ በኦሮሞ ኮንግረስ መሪ በሆነው በመራራ ጉዲና የተሰጠው መግለጫ አሳፋሪና ሰውየውን አላዋቂ የሚያደርገው ነው። መራራ ጉዲና በተለም በአብዮቱ ወቅት ከመኢሶን ጎን በመሰለፍ ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት ይታገል ነበር እየተባለ የሚወደስና፣ እዚህም ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ እየተጋበዘ አንዳንንድ ያልተብራሩ ገለጻዎች በመስጠት ይታወቃል። ይሁንና ግን እንደዚህ ዐይነቱ አሳፋሪ ተግባር ላይ ይሰማራል ብሎ ያሰበም የገመትም የለም። ከዚህ በላይ „ጦርነቱ በድል ቢጠናቀቅም የኦሮሞ ጥያቄ መልስ እስካላገኘ ድረስ ችግሩ ሊፈታ አይችልም“  በማለት የተናገረው  የቱን ያህል ኢ-ሰብአዊ እንደሆነና የፖለቲካ ትርጉምንም በደንብ እንዳልተረዳ ነው ያረጋገጠው። ለማንኛውም ማንነቱን አስታውቋል። እሱ የፖለቲካ መምህር በነበረበት ጊዜም ያሰለጠናቸው ሰዎች የሚሰጡትን ትንተናና በአገራችንም ምድር በዚህ አማካይነት የሚካሄደውን የከሰረ ፖለቲካ ስንመለከት አገራችን የቱን ያህል ብቃትነት በሌላቸውና ምሁራዊና የተወሳሰበ ትንተና መስጠት በማይችሉ ኃይሎች እንደምትሰቃይ እንገነዘባለን።

ይህንን ትተን የሚነሳው ጥያቄ ህውሃት 27 ዓመት ያህል አገራችንን ረግጦ ሲገዛና የክልል ፖለቲካ በማካሄድ ሁለ-ገብ ጦርነት ሲያካሄድ ይህንን ሁሉ ድርጊት ብቻውን ነበር ወይ የሚፈጽመው? ከበስተጀርባው ሌላስ ኃይል ነበር ወይ? ዛሬም አለ ወይ? ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬም የሚካሄደው ጦርነት በእርግጥስ የኢትዮጵያውያን ጦርነት ነው? ወይስ ከውጭ በተቀነባበረ መልክ በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ የውክልና ጦርነት ነው ወይ? ይህንን ጉዳይ በቅጡ መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በዚህ ላይ በቂ ግንዛቤ እስከሌለ ድረስ የህውሃት ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ወይም ደግሞ አመራሩን በቁጥጥር ስር ማዋሉ በብቻው በቂ መልስ አይደለም። በዚህም ብቻ በአገራችን ምድር ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ዘላቂ ሰላምና ተከታታይነት የሚኖረው ህብረተሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይኖራል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው።

     ጦርነቱ የኢትዮጵያውያን አይደለም፣ ጦርነቱ የአሜሪካን፣ የአውሮፓና የአረቦች ጦርነት ነው!!

ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በጦርነት የምትማቅቀው አፍሪካ ብሎ በፈረንጆች አቆጣጠር 2017 ዓ.ም በድረ-ገጾች ላይ ያሰራጨውን ጽሁፉን አስመልክቶ እንደዚሁ በህዳር ወር 2017 ዓ.ም በሰጠሁት ሰፊ ትችትና መልስ ላይ፣ ጦርነቱ የአፍሪካውያን ሳይሆን የአሜሪካንና የአውሮፕያውያን ነው በማለት ለማረጋገጥ ሞክሬያለሁ። ይህንን አመለካከቱን እንደገና በመድገም ከረጅም ወራት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በሚኖረው በተለይም በአማራው ብሄረሰብ ላይ ያነጣጠረውን ጦርነትና፣ ቀደም ብሎም አገራችን የመበታተን አደጋ ላይ ናት ብሎ በመጻፍ ጦርነቱ በውስጥ ኃይሎች ብቻ እንደሚካሄድና የውጭ ኃይልም የግዴታ ጣልቃ በመግባት አገራችንን ከመበታተን ማዳን ያለበትና ታሪካዊ ግዴታም አለበት ብሎ ያቀረበው አቤቱታ የሚያረጋገጠው ሻለቃውም ሆነ አብዛኛው በፖለቲካ ዓለም ውስጥ እሳተፋለሁ የሚለው ኢትዮጵያዊ የቱን ያህል በዓለም ላይ የሚካሄደው ጦርነትና ሶፊስታዊ ፖለቲካ ያልገባቸው መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው።  እንደዚህ ብሎም ማሰብና ይህንን የመሰለውን ሀተታ መሰል ጽሁፍ በማቅረብ ወጣቱን ማሳሳት ለስልጣኔና ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገውን ትግል ማጨናገፍ ብቻ ሳይሆን የአንድ ህዝብ ዕድል በውጭ ኃይሎች ላይ የተንጠለጠለ ነው ብሎ እንደማሰብ ይቆጠራል። ስለሆነም እኛ ጥቁር ኢትዮጵያውያን ከጦርነት የምንላቀቀውና ነፃ ለመውጣት የምንችለው በነጭ ኦሊጋርኪው መደብ ፈቃድ ብቻ ነው ብሎ እንደማመን ይቆጠራል። ያለንም አማራጭ በራሳችን ላይ መተማመንና ምሁራዊ ኃይላችንን በማጠናከር የጠነከረችና የተከበረች ኢትዮጵያን መገንባት ሳይሆን በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጉያ ስር የምትማቅቅና የምትሽመደመድ አገር መመስረት ነው የሚል ነው። አዲስ የፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና፣ እንዲሁም ደግሞ የነፃነትና የፍትህ ቲዎሪ እየተማርን ነው ማለት ነው። የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ሳይሆን ጥቁር የሚባለው ፍጡር በአፈጣጠሩ የተረገመ ስለሆነና ሳይንስና ቴክንሎጂዎችንም መፍተር ስለማይችል ያለው አማራጭ የነጭን የበላይነት መቀበልና ትዕዛዙንም መፈጸም ብቻ ነው ወደ ሚለው ያመራናል።

ለማንኛውም እ.አ. አ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ላይ የተዋቀረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሚሊታሪያዊና ባህላዊ አወቃቀር በምንመረምርበት ጊዜ ሳይንሳዊ የፖለቲካ ቲዎሪ እንደሚያረጋግጠው በአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አህጉሮችን አገሮች ውስጥ በጎሳም ሆነ በሃይማኖት ስም ተሳቦ የሚካሄደው ጦርነት በመሰረቱ የውክልና ጦርነት ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በሚሊታሪ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ የበላይነቱን ሲቀዳጅ ሆን ብሎ የተያያዘው ኮሙኒዝምን ለመዋጋት በሚል ሽፋን ስር የበላይነቱን ለማስፋፋት የግዴታ ጦርነትን በአፍሪካ ምድርና በተለይም በቪትናምና በካምቦጃ ማስፋፋት ነበረበት። የጦርነትን ታሪክ ስንመለከት በአሜሪካን ምድር ከ1945 ዓ.ም በፊትም ሆነ በኋላ፣ በአውሮፓ ምድር ደግሞ ከ1945 ዓ.ም በኋላ በእነዚህ አገሮች ውስጥ በአገሮች መሀከልም ሆነ በውስጥ የሚካሄድ ጦርነት በፍጹም አልታየም፤ በግልጽም ይታወቃል። ይህም ማለት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ጦርነት ዓለም አቀፋዊ የሆነበትና፣ በተለይም ደግሞ አፍሪካ በጦርነት እንድትማቅቅ የተደረገው ካለምክንያት አይደለም። ጦርነቱ በሙሉ የውክልና ጦርነት ወይሞ ደግሞ በተለይም በአሜሪካን፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ መንግስታትና የጥሬ-ሀብትን በሚቀራመቱ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች የሚካሄድ ጦርነት ነው። ይህም ጉዳይ በTom Burgis, The Looting Machine በሚለው መጽሀፉና ክሪቲካል አመለካከት ባላቸው የአውሮፓውያናንና የአሜሪካን ምሁራን የተብራራና የተረጋገጠ ነው። ስለሆነም በአውሮፓና በአሜሪካ ምድር 70 ዓመት ያህል ሰላም ሲሰፍንና እነዚሁ አህጉራት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ኢኮኖሚ ሲገነቡ የአፍሪካ ህዝብ በጦርነት በመጠመድ ጦርነትን ባህሉ እንዲያደርገውና የኑሮውም ፍልስፍና በማድረግ ውስጣዊ ኃይሉን በማስተባበርና በማጠናከር አገሩን መገንባትና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆን የተደረገው በአሜሪካንና በአውሮፓውያን የፖለቲካ ኤሊትና የሚሊታሪና የኢንዱስትሪ ትስስር ምክንያት ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን በአገራችን ምድር የተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር ቀጥተኛ አሻጥር እንደመስራት የሚቆጠር ብቻ ሳይሆን፣ ህዝባችንም ዕውነተኛ ስልጣኔን በዚህም በዚያም ብሎ መሰናክል መስራት ነው።

ጉዳዩን ግልጽና ብዙዎቹም እንዲረዱት ለማድረግ አንዳንድ መሰረታዊ ጉዳዮችን ማንሳቱ ያስፈልጋል። በተለይም አብዛኛው ምሁር ነኝ ባይ ኢትዮጵያዊ በአንድ አገር ውስጥ መንግስትና ህብረተሰብ እንዴት እንደሚመሰረቱ፣ መንግስትስ ማለት ምን ማለት ነው? ሚናውስ ምንድነው? በሚለው ላይ በቂ ጥናት ስለማያደርጉና ግንዛቤ ስለሌላቸው የዓለምን ፖለቲካና በተለይም የአገራችንን ዕድል በየዋህነት መነጽር ነው የሚመለከቱት። በሚስጡትም ከሳይንስ ውጭና በቲዎሪ ባልተደገፈ ትንተና ብዙ ወጣቶችን እያሳሳቱና ዕውነተኛው በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ ኃይል እንዳይዳብር አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ከፍተኛ መሰናክል እየፈጠሩ ነው።  መሰረተ-ሃሳቡን የበለጠ ለመገንዘብ በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተቋቋሙትም ሆነ የተገነቡት መንግስታት ከውስጥ ከታች ወደላይ(Organic Grwoth) በትግልና በቲዎሪ፣ በአንዳች ፍልፍናና ሳይንስ በመደገፍና በመብላላት የተገነቡ ሳይሆን ከውጭ በመጣ አተሳሰብ፣ የሚሊታሪና የፖሊስ፣ እንዲሁም የሲቪል ቢሮክራሲ ርዕዮተ-ዓለም በመደገፍና በመመከር፣ እንዲሁም በመሰልጠን ነው። ይህም ማለት ከመጀመሪያውኑ እንደ አውሮፓው ዐይነት ከታች ወደ ላይ በስራ-ክፍል በዳበረ ኢኮኖሚ፣ በከተማዎች ግንባታ ላይ በተመረኮዘ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገነባብን ሊያመቻቹ በሚችሉና ብቃትነት ባላቸው ተቋማት(Institutions) ላይ በመመርኮዝና ውስጣዊ-ኃይሉ ጠንካራና ተንቀሳቃሽ በሆነና በተገለጸለት የከበርቴ መደብ በመደገፍ  ሳይሆን መንግስታት የተመሰረቱት፣ በተለይም በእርሻ ወይም በአደን ላይ በመሰማራት ላይ በሚንቀሳቀስና ከእጅ ወደ አፍ ላይ በሚደገፍ ላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ነው ከላይ ወደ ታች እንዲጫን የተደረገው። በሌላ አነጋገር፣ በአውሮፓ ምድር የመንግስታትና የህብረተሰብ አገነባብ አነሰም በዛም የተፈጥሮን ህግ ዐይነት ዕድገት በሚመስል መንገድ ሱጓዝ፣ ወደ አገራችንና ወደ ተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ስንመጣ የመንግስታት መኪና አወቃቀር ተፈጥሮአዊ አካሄድን ያልተከተለና በምንም ዐይነት ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመች አይደለም። በዚህ ላይ በአውሮፓ ምድር በምርጫ ምልክ 70 ዓመት ያህል የአገዛዝ ለውጥ ሲካሄድ በአፍሪካ ምድር በአሜሪካና በተቀሩት የአውሮፓ የስለላ ድርጅቶች አማካይነት ከስደሳ በላይ የሚቆጠሩ የአገዛዝ ግልበጣዎችና የባለስልጣናትም ግድያዎች ተካሂደዋል። እነዚህን ሁሉ መካድ ከፍተኛ የሆነ ስትራቴጂክ ስህተት መስራት ብቻ ሳይሆን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜም የስልጣኔውን በር መዝጋት ነው።

ይህንን ትተን ወደሌሎች ዕውቀት ወደሚባሉት ነገሮች ስንመጣ የተማርናቸውና ዛሬም በየትምህርትቤቶችና በየዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት ትምህርቶች፣ ማለትም ከተፈጥሮ ሳይንስ እስከ ኢኮኖሚክስና ሶስዮሎጂ፣ እንዲሁም ፖለቲካ ሳይንስ ድረስ ከውጭ የመጡና ከእየአገሩ ሁኔታ ጋር ተጣጥመው እያንዳንዱን አገር በጠነካራ መሰረት ላይ እንዲገነባና ባህላዊ ኃይል እንዲኖረው የሚያደርጉ ሳይሆኑ ለውጭ ኃይል፣ በተለይም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አፈቀላጤ የሚሆንና ሽንጡን ገትሮ የሚታገል የንዑስ ከበርቴ ኃይል ማፍራትና ወደ ውስጥ ሁለ-ገብ የሆነ የህብረተሰብ ግንባታ እንዳይካሄድ ማድረግ ነው። እዚህ ላይ አለመግባባትን ለማስወገድ ከውጭ የሚመጣው ዕውቀት በሙሉ አሳሳች ነው የሚል ሳይሆን፣ በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉት ትምህርቶች በክስተት ላይ ተመስርተው የተጻፉ በመሆናቸው ኢኮኖሚክስን የሚማረው ተማሪ ኢኮኖሚክስ በአገር ግንባታ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ሚናና ተቀዳሚ ተግባሩስ ምን ነገር እንደሆነ ከመጀመሪያውኑ እንዳያውቅ ይደረጋል።  በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በገበያ ኢኮኖሚ ህግ፣ በአቅራቢና በጠያቂ መሀከል በሚደረግ ድርድርና በገበያ ኃይሎች(Market Forces) አማካይነት ብቻ ነው ብሎ እንዲማር በማድረግ፣ ኢኮኖሚ ከፍልስፍና፣ ከባህል፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ደግሞ ከከተማዎች ግንባታና ከባቡር ሃዲድ ምስረታና ግንባታ ውጭ ተነጥሎ እንዲታይ በመደረግ ተማሪው ከመጀመሪያውኑ የካፒታሊዝምን ዕድገት ሎጂክ እንዳይረዳ ይደረጋል። ስለሆነም አንድ ተማሪ መማርና ማወቅ ያለበት በተለያዩ ፈላስፋዎችና የፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ጠቢባን የተደረሱ፣ ለምሳሌ ኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስንና በካርል ማርክስ የተጻፈውን ስለካፒታሊዝም ከታች ወደ ላይ ዕድገትን የሚያሳየውን Das Capital ሌሎችን በእነ ፍሪድሪሽ ሊስትና በሌሎችም ምሁራን የተጻፉትን፣  በተለይም ወደ ውስጥ እንዴት የአንድ አገር ኢኮኖሚና ማህበረሰብ እንደሚገነቡ የሚያስተምሩ መጽሀፎችና አያሌ ምሁራን የደረሱትን መመሪያዎች እንዳይማር ይደረጋል። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ በተኮላሽ መልክ የሰለጠነ ኢኮኖሚስትና በፖለቲካ ሳይንስ የሰለጠነ ኤሊት የውጭ ኃይሎች ታዛዥ ከመሆንና ወደ ውስጥ ሁለ-ገብ የሆነ ጦርነት ከማካሄድ በስተቀር ሌላ ተግባር በፍጹም ሊኖረው አይችልም። ይህ ብቻ ሳይሆን በፍልስፍና፣ በሶስይሎጂ፣ በሳይንስና በቲዎሪ በደንብ ያልተኮተኮተ ቢሮክራሲያዊ ኃይልና የአካዴሚክ ምሩቅ የአገሩን ህዝብ መናቅ ይጀምራል። እሴቱንና ባህሉን እንዲረግጥ ይደረጋል።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ወደ ሁለት ትውልድ የሚያስቆጥረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ስንመለከትና በተለያዩ ጊዜያት አገራችንን ሲገዟት የነበሩትን አገዛዞች ስነ-ልቦና፣ ሞራላዊ ብቃትና የፖለቲካ ስልት ስንመለከት ለምን አገራችን በእንደዚህ ዐይነቱ ትርምስ ውስጥ ለመውደቅ እንደበቃች መረዳቱ ይህን ያህልም የሚከብድ አይመስለኝም። ይሁንና ግን ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ ለመረዳት አንድ ሰውም ሆነ ድርጅት በተከታታይ 20ና 30 ዓመታት ሳያቋርጥ ማጥናትና መመራመር አለበት። ይህንን ሲያደርግ ብቻ ነው የአገራችንንም ሆነ የተቀሩትን አፍሪካ አገሮች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ባህላዊ፣ የአካባቢና የስነ-ልቦና ቀውሶችንና ጦርነቶች በደንብ ለመገንዘብ የሚችለውና መፍትሄም ለመስጠት የሚሞክረው። ስለሆነም በቂ ግንዛቤና የተወሳሰበ ዕውቀት ያለው ምሁራዊ ኃይልና በየጊዜው የሚከሰቱትን አዳዲስ ችግሮች በደንብ የሚያጠናና የሚመራመር የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች በሙሉ የተጠኑና በደንብ ግንዛቤ የሚያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውስጥ ሰላምን የሚያመጡና ፈጠራዊ ስራዎችንም የሚያመቻቹ ይሆናሉ ማለት ነው።

ሰለሆነም ወደ ሃምሳ ዓመት የሚጠጋው በአገራችን ምድር በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚካሄደው ጦረነት፣ በአንድ በኩል ከውስጥ ያለንን የምሁራዊ ብቃትነት ችግር የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በደንብ የተደራጀና ብሄራዊ ባህርይ ያለው መንግስትና አገር ወዳድ የሆነ ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር በቀላሉ በውጭ ኃይሎች እንደሚጠመዝዝና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ነው።  ከዚህም በላይ የህብረተሰብን አገነባብ ሎጂክንና የፖለቲካ ኢኮኖሚክስን ህግ ሳይረዳ አንድ አገዛዝ ተግባራዊ የሚያደርገው ከውጭ የመጣና በውጭ ኃይሎች የሚጫን ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በአንድ አገር ውስጥ ሚዛናዊ የጎደለው፣ በተለይም ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያደላና የተወሰነውን የህብረተሰብ ጥቅም ብቻ የሚጠቀም የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ ለአፈንጋጮችና ሌላ አጀንዳ ላላቸው ኃይሎች ምክንያት ሊፈጥር ይችላል። ከ1945 ዓ.ም  በፊት የነበረውን የአገራችንን የፖለቲካና የህብረተሰብ ሁኔታና አወቃቀር ስንመለከት በጊዜው የብሄረሰብ ጥያቄና የብሄረሰብ እንቅስቃሴ የሚታወቅ አልነበረም። የብሄረሰብ ጥያቄና የጭቆና ጉዳይ የሚባለው ፈሊጥ ከ1950ዎቹ ዓ.ም መጨረሻ በኋላ በተለይም በ1960ዎቹ የተነሳና እንደመሰረታዊ ጥያቄ የተወሰደና በተሳሳተ መልክ በመተርጎም የማያስፈልግ ንትርክ ውስጥና እንዲያም ሲል ጦርነት ውስጥ የከተተን ነው። በፖለቲካው መስክ የግንባር ቀደምትነትን ሚና የያዙት የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች የብሄረሰብን ጥያቄ እንደመሰረታዊ ጥያቄ ሲያነሱና ሲሰብኩ ያላጠኑትና ያላጤኑት ነገር በአውሮፓ ምድር ህብረ-ብሄር እንዴት እንደተመሰረታና ካፒታሊዝም ከታች ወደ ላይ በተወሳሰበ መልክ እንደተገነባ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የተማሪው እንስቃሴ መሪዎች ከ1960ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፍሪያማ በሆነ መልክ የተካሄደውን ስለካፒታሊዝም ዕድገትና ስለህበረተሰብአዊ ለውጥ (Transformation Debate) ክርከር አይ አያውቁም ወይም ደግሞ በማወቅ ዘንግተው አልፈውታል። ከዚህም በላይ ካፒታሊዝም ከማደጉ በፊት በአውሮፓ ምድር በፍልስፍና፣ በቴዎሎጂ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በተለይም በፖለቲካው መስክ ስለሊበራልዚምና ስለገበያ ኢኮኖሚ፣ ስለመንግስት ሚናና ስለ ግለሰብአዊ ነፃነት፣ በእነዚህ ዙሪያ የተካሄደውን ምርምርና ጥናት፣ ይህም በየመንግስታቱ ላይ የነበረውን ተፅዕኖና በፖሊሲ ቀረፃ ላይ የነበረውን ሚና አይ አያውቁም ወይም ደግሞ በማወቅ አስፈላጊ አይደለም በማለት እረግጠው አልፈውታል። ከዚህም በላይ ካፒታሊዝም ካደገና ዓለም አቀፋዊ መልክ እየያዘ ከመጣ ወዲህ እንደኛ ባሉት መንግስታትና አገሮች ላይ ያስከተለውን አሉታዊ የህብረተሰብ አወቃቀርና የተበላሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ሊያስከትል የሚችለውን በተጨባጭ መልክ የሚታየውን ሁኔታ በደንብ አልተገነዘቡም፤ በታወቁ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ ምሁራን፣ እንዲሁም ክሪቲካል አመለካከት ባላቸው በአውሮፓና በአሜሪካን ምሁራን የተደረሱትን መጽሀፎች ጠጋ ብለው በመመልከት የማጥናትና የመመራመር ዕድል አላገኙም።

እነዚህን ነገሮች ማጤንና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማካተትና መመርመር ያልቻሉት የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ሳያውቁት መንገዱን ለእርስ በርስ ሽኩቻና እንዲያም ሲል መንገዱን ለጦርነት ነው ያመቻቹት ማለት ይቻላል። ለማለት የተፈለገው ከውጭ በተቆነፀለ መልክ የገባው ትምህርት የሚመስልና ኢኮኖሚ ፖሊሲና ያልተስተካከለ ዕድገት አመፀኛና(Irrational Forces) የታሪክን ሂደት ለሚያጣጥሙ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። በዚህ ላይ ከህብረተሰብ ዕድገት ወይም ከህብረ-ብሄር ግንባታና ከአገራችን የፖለቲካ ባህል እጦት ጋር ሳይገናዘብ የተወረወረው የብሄረሰብ ጥያቄ የሚሉት ነገር ለፅንፈኛ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን ለውጭ ኃይሎችም በቀላሉ ሊጠመዝዟቸው የሚችሉ ኃይሎችን በማግኘትና እነሱንም መሰላል በማድረግ ያለ የሌለ ኃይላችንን ወደ አገር ግንባታ ከማድረግ ይልቅ ወደ እርስ በእርስ ግብግብ ላይ እንድናውለው ለማድረግ ችለናል።

ከዚህ ትንትና ስንነሳ፣ ሻብያ በአጀማመሩም ባይሆን፣ የኋላ ኋላ በአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት የወደቀና በአረቦች የሚደገፍ ነው። የሚካሄደውም ጦርነት በእነሱ እየተደገፈ ነበር። መለሰ ዜናዊና ግብረ-አበሮችም የእንግሊዝ የስለላ ድርጅትና የኋላ ኋላ ደግሞ የሲአይኤ ምልምሎች ናቸው። የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት(OLF) የሚባለውም በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የስለላ ድርጅቶችና የፕሮቴስታንት ቸርች የሚደገፍ ነበር። አሜሪካንም ሆነ አውሮፓውያን የነፃ አውጭ ለሚባሉት ድርጅቶች የሚሰጧቸው ዕርዳታ ተጨቆኑ የሚባሉ ብሄረሰቦችን በእርግጥ ነፃ ለማውጣትና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ ሳይሆን አገራችንን በጦርነት በመወጠር እንድትበታተን ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ የአውሮፓና የአሜሪካን የፖለቲካ ኤሊቶች፣ ከዴሞክራቶች፣ እስከ ሶሻል ዲሞክራቶችና ኮንሰርቫቲቮች ድረስ የሚከተሉት ፖለቲካ በመሰረቱ እነካንታና ሌሎች የፖለቲካ ፈላስፋ ምሁራን የነደፉትን በአገሮች መሀከል ሊኖር የሚገባውን በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት የሚጻረር ነው። የአሜሪካንና የአውሮፓ የፖለቲካ ኤሊትም ሆነ የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ የሚከተሉት ፖሊሲ አብዛኛውን ጊዜ የተወሰደው ከእንግሊዙ የሊበራል ፈላስፎች፣ በተለይም ከእነ ሆበስ ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ፍልስፍና መሰረት ማንኛውንም አገር እንደተቀናቃኝና እንደዋና ጠላት አድርጎ  ማየት በተለይም የእንግሊዞች የውጭ ፖሊሲና ከባርያ ንግድና ከቅኝ-ግዛት ፖሊሲያቸው ጋር የተያያዘና የነጭ ኦሊጋርኪውን መደብ የበላይነት የሚያሰፍንና፣ በዚያም መጠንም በየአገሮች ውስጥ ጤናማማ ተከታታይነት ያለው ዕድገት እንዳይኖር የሚያደርግ የውጭ ፖሊሲ ነው። የአሜሪካንን የውጭም ሆነ  የውስጥ ፖለቲካ ስንመለከት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው ክፍለ-ዘመን በአራቱ ታይራኖች በአቴን የሰፈነውን በጦርነትና በስግብግብነት ላይ የተመሰረተውን ሁሉንም ለእኔ ይገባኛልና ካለኔ ፈቃድ ምንም ነገር ለማድረግ አትችሉም የሚለውን የአገዛዝ ፍልስፍና የሚያረጋግጥ ነው። ፕላቶ ሶክራተስን በመመሰል ጆርጂያስ በሚለውና በቀደመው ክርክሩ የሚያነሳውና ለማስተማር የሚጥረው በሰብአዊነትና በፍትሃዊነት ላይ እንዲሁም በጦርነትና በስግብግብነት(Power and Greed) በተመሰረተው መሀክል ያለውን የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነት ነው። ስለሆነም አሜሪካን ቀደም ብሎም  በኋላ የኢምፔሪያሊዝምነት ሚና ከቀተቀዳጀ ጀምሮ የሚያካሂደው የውጭ ፖለቲካ በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የአቴኑ ገዢ የነበረው እነ ፐሪክለስ ያካሂዱ የነበረውን በበላይነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ከሲአይኤ በስተቀር ሌላ 17 ያህል የመንግስ አካል የሆኑ የስለላ ድርጅቶችና የሚሊታሪውና የፖሊሱ አደረጃጀት ሁኔታ በደንብ የሚያረጋግጡ ናቸው። ሲአይኤ ብቻ በዓመት $100 ቢሊዮን ባጀት ሲኖረው፣ የሚሊታሪው ባጀት ደግሞ በዓመት $700 ቢሊዮን ያህል ነው። ከዚህም በላይ ትላልቆቹ የጦር መሳሪያ ፋብቭሪካዎች በአሜሪካን ምድር የሚገኙና በሺህ ድሮች ከመንግስቱ መኪና ጋር፣  በተለይም ከፔንታጎን ጋር የተያያዙ ናቸው። የእነዚህ ሁሉ ተግባር ሌላ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነት የሚመጣበትን ምክንያቶች መፍጠርና  እንደኛ የመሳሰሉ አገሮችን  ጦርነት ውስጥ እንድንገባ በማድረግ  ያለ የሌለ ኃይላችንና ሀብታችንን እንድንጨርስ ማድረግ ነው። የአሜሪካ መንግስት ለሚሊታሪውና ለስለላ ድርጅቱ ይህንን ያህል ገንዘብ እየመደበ በሌላ ወገን ግን የህብረተሰቡን ንቃተ-ህሊና ለማዳበር፣ የስራ መስክ ለመክፈት፣ለማህበራዊና ለጤንነት፣ እንዲሁም ደግሞ ለትምህርት የሚያወጣው ወጭ ዝቅተኛ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳና በልዩ ዓይነት መልከ በተዋቀረው የአሜሪካን ካፒታሊዝም የአመራረትና የፍጆታ አጠቃቀም ሁኔታ የተነሳ በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ ጥቂት የማይባል ህዝብ በጣም አደገኛ(Aggressive) አስተሳሰብ አለው። በየቀኑ ብቻ በጠቅላላው አሜሪካን ምድር ወደ 700 ያህል ሰው በጠብመንጃ እንደሚገደል ይነገራል። ቢያንስ ግማሽ ያህል የሚሆነው የአሜሪካን ህዝብ ንቃተ-ህሊናው በጣም ደካማ እንደሆነ ይነገራል። ስለሆነም ነው በአሁኑ ምርጫ 70 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕን የመመረጠው። ይህም የሚያረጋግጠው ህዝቡ ለመመረጥ ብሎ የሚመርጥ እንጅ ይህን ያህልም ስለ ፖለቲካና ስነ-ስርዓት ስላለው ህብረተሰብና ስለ መንግስት ሚና የተረዳ በመሆኑ አይደለም። ይህንን ዐይነቱን ሊበራል ዲሞክራሲና ነፃ ገበያ ብለው ይነግሩናል። የዓለም ማህበረሰብም ይህንን ዐይነቱን የህብረተሰብ ሞድሌ መከተልና ተግባራዊ ማድረግ አለበት ይሉናል። ይሁንና ግን ከፕላቶን እስከ ላይብኒዝ ያሉት ፈላስፋዎች በሙሉ እንደዚህ ዐይነቱ በስግብግብነትና በአመጽ ላይ የተመሰረተ አገዛዝና ህብረተሰብ በዘለዓለማዊ ጦርነት እንደሚኖሩ ነው። ስለሆነም ይሉናል፣ የሰው ልጅ ከእንደዚህ ዐይነቱ አደገኛ አስተሳሰብ ለመላቀቅ የግዴታ የማሰብ-ኃይሉን በመጠቀም ፍትሃዊነት የሚኖርበት ስርዓት ለመመስረት መጣር አለበት። በየጊዜውም ራሱን መጠየቅና መመርመር አለበት ይሉናል። በአገራችን ምድር ከአርባ ዓመታት በላይ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱትን ድርጅቶችና የየመንግስቶቻችን አወቃቀርና የፖለቲካ ፍልስፍና በምንመረምርበት ጊዜ መሰረቱ በዚሁ ዐይነቱ የአሜሪካ አመጸኛ የፖለቲካ ፍልስፍና የተዋቀረ ነው። በሊበራል ስም እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሰው  አገር ወዳድ ነኝ እያለ የሚያስቸግረንና ወጣቱን የሚያሳስተው ሁሉ ስልጣን ከወጣ በኋላ የመጨረሻ መጨረሻ እንደዚህ ዐይነቱን ጨቋኝ ስርዓት ለመመስረት ነው። የአገራችንን ሁኔታ ለየት የሚያረገው ነገር ይህንን ዐይነቱን አግሪሲብ ፖለቲካና መንግስታዊ አደረጃጀት የሚቃወምና የተሻለ አስተሳሰብ አለመኖሩ ነው። ከዚህም በላይ ይህ ዐይነቱ ፍልስፍና በአገራችን ፖለቲከኞች ተቀባይነቱን ያገኘው ፊዩዳላዊ በሆነ የአስተሳሰብ ስሌት ውስጥ ነው። ዘመናዊ የሚመስሉና ፊዩዳላዊ አስተሳሰቦች አንድ ላይ ሲጣመሩ ደግሞ በጣም አደገኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ይፈጥራሉ። ይህንን በሚመለከት ሰፊ ጥናት ተካሂዷል።

ስለሆነም በአገራችን ምድር አብዮቱ ከፈነዳ ጀምሮ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትና ዛሬም አገራችን ያለችበት ሁኔታ የዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና የተበላሽ ፖሊሲ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በአብዮቱ ዘመን የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአሜሪካንና የእንግሊዝ የስለላ ድርጅትና በተለይም በግብጽ የተደገፈ ነበር። አንዳንድ ተራማጅ ነን ባዮች በሲአይኤና በግብጽ የስለላ ድርጅት በመመልመል አብዮቱ እንዲጨናገፍ ጦርነት ከፍተው እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በጊዜው በቀይና በነጭ ሽብር ተሳቦ የሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት የውጭ ኃይሎች እንደነበሩበት ግልጽ ነበር። አብዮቱም ከሸፈ ከተባለ በኋላ በዚያን ዘመን ለአሜሪካን ጥሩ ስራ ሰሩ የተባሉ ኃይሎች ፓስፖርት እየተሰጣቸው ነው አሜሪካ እንዲገቡ የተደረገው። ሌሎች ደግሞ ክሱዳን በአውሮፕላን በመወሰድ እዚያው እንዲኖሩ ሁሉ ነገር ተመቻችቶላቸውል።

አብዮቱ ከከሸፈም በኋላ ወያኔዎች ስልጣን ላይ ሲወጡ በመሰረቱ የትግራይን ብሄረሰብ ነፃ ለማውጣት ሳይሆን  የአሜሪካንንና የግብረ-አበሮችን ትዕዛዝ ማስፈጸም ነው። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ በመባል የሚታውና የኋላ ኋላ ደግሞ አልሻባብን ለመዋጋት ተብሎ በሱማሌ ውስጥ የሚካሄደው የጣልቃ-ገብ ጦርነት የዚህ ስትራቴጂ አንድ አካል ነው። ጦርነትን በአፍሪካ ቀንድና በአካባቢው አገሮች ማስፋፋትና እነዚህን አገሮች በጦርነት ወጥሮ መያዝ ነው። በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲውን ስንመለከት የውጭ ኃይሎች ዋና ዓላማ አንድ ወጥ የሆነ፣ ግን ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈና ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዳይገነባና የህብረ-ብሄር መሰረት እንዳይጣል የሚያደርግ አብዛኛዎችን የአፍሪካና የላቲን አሜሪካን አገሮችን መቀመቅ ውስጥ የከተተና በዕዳም እንዲተበተቡ ያደረገና የሚያደርግ ነው። ይህም ማለት፣ ወያኔ በዓለም የገንዘብ ድርጅተና(IMF) በዓለም ባንክ(WB)፣ ባጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው በመባል በሚታወቀው እየተመከረና ግፊት እየተደረገበት ተግባራዊ ያደረገው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብሄራዊ ሀብትን(National Wealth) የመፍጠር ኃይል የለውም። የስራ-ክፍፍል እንዲዳብር አያደርግም። ለሳይንስና ለቴኮኖሎጂ መሰረት የሚጥል አይደለም። ለተቋማት መመስረት የሚሆኑ መሰረቶች እንዲገነቡ አያመቻችም። አንድን አገር እንደማህበረሰብ የሚያይ አይደለም። ስለሆነም  መሆንና መቅደም የሚገባውቸውን ነገር ትቶ የህዝብን ፍላጎት በማያሟላና ለአገር ግንባታ በማያመቹ ነጎር ላይ መንግስትና ህዝብ እንዲያተኩሩ በማድረግ ያልታቀደ ማህበራዊ ቀውስና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲፈጠር ያደርጋል። የፖሊሲው ዋና ዓላማ አንዳንድ ፖሊሲ ነክ ነገሮችን በመለወጥ ብቻ ኢኮኖሚው በምርት ክንዋኔ ላይ ሳይሆን በንግድና በአገልግሎት ላይ ብቻ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። ይህ ዐይነቱ ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በካፒታሊዝም የህብረ-ብሄርና የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ተግባራዊ የሆነበት ጊዜ አልነበረም። ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በካፒታሊስት አገሮች የተካሄደውን የአገር ግንባታና የካፒታሊምን ዕድገት በምንመረምርበት ጊዜ መንግስታት ተግባራዊ ያደርጓቸው የነበሩ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮሩና በከፍተኛ ዕውቀት ላይ የተመረኮዙ ነበሩ ማለት ይቻላል። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ህወሃት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ፣ እንዲሁም ደግሞ በሌሎች የውጭ አገር ኤክስፐርቶች እየተመከረና እየተገፋ ተግባራዊ ያደረገው  የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዘራፊ የሆነን መንግስትና(Predatory State) ሳይሰራና ሳይፈጥር በቀላሉ ሀብታም ሊሆን የቻለ የህብረተሰብ ክፍልነ የፈጠረ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ  ነው በአገራችን ምድር ያልተስተካከለና ሀብትን የሚያወድም፣ እንዲሁም የአካባቢን ብክለት ያስከተለ ሁኔታ ሊከሰት የቻለው። ይህ ዐይነቱ ይበልጥ በንግድና በአገልግሎት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ዕድገት በህዝባችንም ላይ በስነ-ልቦናው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር አጭበርባሪዎችና ማጅራት መቺዎች እንደ አሸን የፈለቁበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህም ማለት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የተከፈተብን ጦርነት ሁለ-ገብና በቀላሉ መፈናፈኛ ያሳጣን ነው። የባህል ውድመትን ያስከተለ ነው። በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ለጋ ልጆች ሕይወታቸው እንዲቀጠፍ ያደረገ ነው። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን የፖለቲካ ክንዋኔ፣ የህብረተሰብ አውቃቀርና የባህል ሁኔታ ውስጥ የውጭ ኃይሎችን ሚና አሳንሶ ማየት ወይም በአገራችን ምድር የተፈጠረው የተወሳሰብ ችግር በአገዛዙ ብቻ እንደተፈጠረ አድርጎ መመልከት ከፖለቲካ ሳይንስ ምርምር ውጭ የሆነ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ነው።

የኢኮኖሚው ፖሊሲውና የክልሉ ፖሊስ በእርግጥም በየክልሉ የጎበዝ አለቃ ስሜት በማሳደር የኢትዮጵያን መፈረካከስ አመቻችቷል ማለት ይቻላል። ከ27 ዓመታት በኋላ ወያኔ እንደሎሚ ተሟጦ ካለቀ በኋላ በአዲስ ኃይል መተካት ነበረበት። ወያኔ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ወደ ትግራይ ክልል ጓዙን ጠቅልሎ ከሄደ በኋላ ከውጭ ኃይሎች ጋር ያለውን ግኑኝነት በፍጹም አላቋረጠም። በዚህ ላይ የጽንፈኛ ኃይሎች ተግብስብሶ መግባትና የፖለቲካ መድረኩን መያዝ በአገራችን ምድር ከፍተኛ ውጥረትን አስከትሏል። የብሄረሰብ ጥያቄ ልዩ ዐይነት ክስተት በመያዝ ጽንፈኛ ኃይሎች እንደፈለጋቸው ከ90% በላይ የሚሆነውን ህዝባችንን እስረኛ በማድረግ እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ተደርገዋል። ባለፉት ሁለት ዐመታት ተኩል በወያኔ እየተደገፈ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት፣ በተለይም በአማራውና በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ላይ ያነጣጠረው ግድያና ቤተክርስቲያናትን ማቃጠል አገራችንን እንይጎዝላቢያ ለማድረግ ከታቀደው ስሌት በመነሳት ነው። የምዕራቡ መንግስታት የስለላ ድርጅቶች በየአገሮች ሰርገው በመግባት የሚያካሂዱት የከፋፍለህ ግዛውና የጦርነት ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው በአገዛዞች ዕውቅና ያላቸው ናቸው ብሎ መናገር ያስቸግራል። የስለላ ድርጅቶች በየጠዋቱ የዜና ብሪፍንግ ለፕሬዚደንቶችና ለጠቅላይ ሚኒስተሮቻቸው የሚያቀርቡት ሀተታ መሰል ነገሮች በራሳቸው ጭንቅላት ውስጥ የሚመረቱና የስለላ ድርጅቶችን የማጠናከር ስትራቴጂ ነው። ከዚህም በላይ በመንግስታት የሚደገፉ የውጭ ፖለቲካን የሚያጠኑ ተቋማት የየአገሩን የህብረተሰብ አወቃቀርና የህዝቦችን የስነ-ልቦና ያውቁ ይመስል የሚያቀርቧቸው „ጥናቶች“ ራሳቸውም መንግስታትን የተሳሳተ ፖለቲካ እንዲከተሉ እያደረጓቸው ነው።  እነዚህ ሁሉ ተቋማት የየአገሩን ሁኔታ ለማወቅ ደግሞ ለጥቅም በተገዙ ከየአገሩ ሰዎች ጋር መረጃ ነክ ነገር ያገኛሉ። በዚህ መልክ እንደኛ በመሳሰሉ አገሮች በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተቀነባበረ ሴራ ሁለ-ገብ ጦርነት ይካሄዳል ማለት ነው።  በዚህህ ዐይነቱ እርኩስ ድርጊት 27 ዓመታት ያህል በውጭ የስለላ ኃይሎች ሲሰራበት የከረመና አገራችንም እንደወንፊት በመሆን ማንኛውም የስለላ ድርጅት የሚገባባትና የፈለገውን ስራ ሰርቶ የሚወጣባት አገር ለመሆን በቅታለች።

ለዚህ ነው የሳውዲ አረብያና የተቀሩት የአረብ አገሮችና የቱርክ፣ እንዲሁም የምዕራብ አውሮፓ የስለላ ድርጅቶች እንደፈለጉ በመግባትና በመውጣት የፈለጉት ስራ መስራት የሚችሉት። ስለሆነም ከብሄረሰብ ግጭት ባሻገር የእስልምና ሃምኖት መስፋፋትና መስጊዶችና ቤተክርስቲያኖች ካለዕቅድና ካለፍላጎት መሰራታቸው የሚያረጋግጠው የቱን ያህል የውጭ ኃይሎች የአገራችንን መፈረካከስ ለማጣደፍ ተንኮለኛ ስራዎችን እንደሚሰሩ ነው። በተለይም በየዓመቱ የእስልምናን ሃይማኖት በዓል ለማክበር ወደ መካ የሚሄዱ አንዳንድ እስላሞች ሲመለሱ በገንዘብ ታጭቀው እንደሚመለሱና መስጊዶችን እንደሚሰሩ የተረጋገጠ ነው። የእነሳውዲ አረብያ ዋና ዓላማ ደግሞ የእስልምናን ሃይማኖት በማስፋፋት ሺፋን ስም ከረጅም ጊዜ አንፃር አብኛውን ህዝብ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በማድረግ የአገራችንን ሀብት ለመቆጣጠር ነው። በመሰረቱ የማንኛውም ሃይማኖት ዓላማ ጭፍን ዕምነትንና አግሪሲቭ ባህርይን ማስፋፋት ሳይሆን ሰላምንና ፍቅርን መስበክ ነው። የአረብ አገሮችን የውስጥ ፖለቲካ ስንመለከት ፖለቲካቸውና ኢኮኖሚያቸው በስራ ላይ የተገነባ ሳይሆን በዘረፋ ላይ ነው። ተፈጥሮ የለገሳቸውን የዘይት ሀብት በመጠቀም በዶላር እንደኛ ያለውን አገር ህዝብ አዕምሮ በማደንዘዝ ተመጽዋች ሆኖ እንዲኖር ማድረግ ነው። ለጦርነትና ለዘረፋ የሚያመች የህብረተሰብ ክፍል በመመልመል ሰፊው ህዝብ ጨልሞበት እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ የአሜሪካኖችም ሆነ የአረብ አገሮች ፖሊሲ በመሰረቱ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚቀናቀን ነው። ዕውነተኛ የሆነ የሊበራል አስተሳሰብ እንዳይስፋፋና እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረው በማድረግ ተፈጥሮ የለገሰውን የመፍጠር ችሎታ በመጠቀም የተረጋጋና የሰለጠን ህብረተሰብ እንዳይገነባ የሚያደርግ ነው።

ነገሩን መቋጠሪያ ለማስያዝ በትግራይ ክልል በስሜን ዕዝ ላይ ሳይታሰብ የተከፈተው ጦርነትና ፋሺሽታዊ ድርጊት ጊዜውን ጠብቆ የፈነዳ ቢሆንም ሎጂካዊ ሂደቱ ከላይ በተጠቀሰ መልክ መታየትና መነበብ ያለበት ጉዳይ ነው። ወያኔና ግብረ-አበሮቹ ከዚያ በመነሳት በአገራችን ምድር አጠቃላይ ጦርነት በመክፈት ለመጨረሻ ጊዜ ለመፋለምና እንድገና ስልጣን ላይ ለመውጣት ነበር። ይሁንና ግን ጀግናው የኢትዮጵያ ወታደር በደረሰበት ጥቃትና በጓዶች መሞት በቀላሉ ሳይደናገጥ ለወያኔና ግብረ-አበሮቹ አስፈላጊውን አፀፋ ለመስጠት ችሏል። በዚህም የተቀነባበረና ስልት የተሞላበት ትግሉ የአገራችን ብሄራዊ ነፃነት በቀላሉ እንደግብጽና እንደሱዳን ለመሳሰሉት መንግስታት ሊደፈር እንዳመይችል አረጋግጧል። ይህ ብቻ ሳይሆን የምዕራቡ መንግስታትና የወያኔ ደጋፊዎች የሆኑ ሁሉ አንዳንድን ነጮች ሀፍረታቸውን ተከናንበዋል። ሰሞኑን እንደምንከታተለው አሜሪካ ወደ 1000 የሚጠጉ ዜጎቼን ማውጣት አለብኝ እያለ ይወተውታል። ከነዚህ ውስጥ ከትግሬ ብሄር-ሰብ የተወለዱና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እንዳሉ ይታወቃል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከአስር በላይ የሚቆጠሩ ትግሬዎች የአሜሪካን ዜግነት እንዳላቸው ይታወቃል። እነዚህ ሰዎች ማንን ወክለውና በምንስ ተግባር ላይ ተሰማርተው ትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱና እንደሚኖሩ አይታወቅም። በግልጽ እንደሚታወቀው የአሜሪካን ዜግነት ያላቸው ከትግሬ ብሄረሰብ የሚወለዱ የትግራይ ክልልም ሆነ አዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎች በኤስክፐርት ስም የተሳሳተ ምክር በመስጠት የአገራችንን ገበሬዎች በተለይም ቡና አምራቹን ቡና እያመረተ እንዲያቀርብ በማድረግ ከሌሎች የእርሻ ተግባራት እንዲታገድ በማድረግ ራሱን መመገብ እንዳይችል አድርገውታል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም የልዩ ልዩ ሰብሎችን ዘር በሞኖፖል በመቆጣጠርና ከውጭ የዘር አምራች ኩባንያዎች ጋር ልይ ግኑኝነት በመፍጠር የአገራችን ገበሬዎች ከውጭ በሚመጣ ዘርና ማዳባሪያ ጥገኛ እንዲሆኑ አድርገዋል። ባጭሩ እነዚህ ሁሉ ኃይሎች በኤክስፐርት ስም በሀብት ዘረፋና ችብቸና ተሰማርተዋል ማለት ይቻላል። ስለሆነም  አይታወቅም።

               የራስን ምንነትና ችሎታ ለማወቅ ያለመቻል የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት !!

ሬኔ ዴካ የሚባለው የ17ኛው ክፍለ-ዘመን ፈላስፋ ሁለት የሚላቸው መሰረተ-ሃሳቦች አሉ። እነሱም ማንኛውም ነገር መጠርጠር፣ ማንኛውም ሰው የሚለውን ነገር ዕውነት ነው ብሎ አምኖ አለመቀበል። ሁለተኛው ደግሞ ራሳን ማወቅ። አንድ ሰው ራሱን ሲያወቅ ወደ ዕውነተኛዉ  ዕውቀት የሚያደርገው ጉዞ አነሰም በዛም ሊቃናለት ይችላል። ሁሉንም የሚጠራጠር እንደዚህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብሎ ራሱን የሚጠይቅ ሰው መጥፎ ነገሮችና ህብረተሰብአዊ ጉዳቶች ከማድረስ ይቆጠባል። ይህ ዐይነቱ ሰው የማመዛዘን ኃይል ወይም ህሊና አለው ማለት ይቻላል።

ከዚህ ስንነሳ ባለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት  የተለያየ ስም ይዘው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ አሊያም ደግሞ የብሄረሰቤ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ የማሰብ ኃይላቸውን ለመጠቀማቸውም  ሆነ ህሊና እንዳላቸው እንድጠራጠር እገደዳለሁ። እዚህ ዐይነቱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ብዙ ምርምር አያስፈልግም። አርባ ዓመት ያህል በኢትዮጵያ ህዝብና በታሪካችን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ድርጊት ራሱ ህያው ማስረጃ ነው። ይሁንና ግን እጅግ በሚያስገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ በወንጀል የተሳተፈና አገር ያከረባበተ፣ ወይም የመንግስትን ምስጢር ለውጭ የስለላ ኃይል አሳልፎ የሰጠ ከደሙ ንጹህ ነኝ፣ ካለኔ በስተቀር ለኢትዮጵያ የሚቆረቆር የለም ብሎ ሽንጡን ገትሮ ሲናገርና ሲጽፍ ስመለከት እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ምንም ዐይነት ሁሊና እንደሌላቸው መገንዘብ እችላለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን  የወንጀል ስራ የሚክዱ ደግሞ በህብረተሰብአቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ሊገነዘቡ የሚችሉ አይደሉም ማለት ነው።

ይህንን ትተን ወደ ህውሃት ጉዳይ ስንመጣ የምንገነዘበው ሀቅ ይህንን ነው። ህወሃት ስልጣን ከመያዙም በፊት ሆነ፣ ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያን 27 የኢትዮጵያን ዕድል በመጥፎ ሁኔታ ሲወስን አንዳችም ላይ ቆሞ እሰራ የነበረውና አሁንም የምሰራው ነገር ትክክል ነው ብሎ ራሱን ጠይቆ አያውቅም። በተለይም ስልጣንን ከተቀዳጀ ጀምሮ በውጭ ኃይሎች ምክርና ትብብር ሆን ብሎ የተያያዘው እንዴት አድርጌ ጠቅላላውን አገሪቱን መቆጣጠር እችላለሁ፣ የምዝበራ ስራም አካሂዳለሁ ብሎ ነው። ይህም ማለት ራሳቸው ታጋዮች  በአፋቸው እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ለሌላ ነገር ሳይሆን ለትርፍና ለምዝበራ ነው። የኛ ዋና ተግባር የተቀረውን የኢትዮጵያ ግዛት በማራቆትና በመመዝበር ታላቋን ትግራይ መመስረትና መገንባት ነው። ይህ ነው የህውሃቶች ፍልስፍና። አብዮታዊ ዲሞክራሲ እየተባለ ተቃዋሚ ነን በሚሉ ኃይሎች የሚወነጀለው የህውሃት አገዛዝና ካድሬዎቹ በመሰረቱ ፍልስፍናቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይሆን ምዝበራና በከፍተኛ ደረጃ ራሳቸውን ማደለብና ከሌላው በልጦ መገኘት ነው።

ይህንን የምዝበራ ፖሊሲያቸውን ዕውን ለማድረግ፣ በመጀምሪያ ደረጃ የክልሉ ፖሊሲ ዐይነተኛ መሳሪያ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የመንግስትን መኪና በተለይም የሚሊታሪውንና የፀጥታውን ክፍል በራሳቸው ቁጥጥር ስር ማድረግ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ለዚህ ምዝበራቸው የሚያመቸውን በነፃ ገበያና በሊበራላይዜሽን ስም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ተዘጋጅቶ የመጣውን የመዋቅር ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ነው። በነዚህ ሶስት አማካይነት ብቻ አገሪቱን በራሳቸው ቁጥጥር ስር ማድረግና የአገሪኢቱን ሀብት መዝረፍ የጀመሩትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ማባለግ የቻሉት። ይህ ዐይነቱ የምዝበራና አገርን የማፈራረስ ሁኔታ መካሄድ የቻለው ደግሞ ፖለቲካ ያገበኛል የሚለው ሁሉ እጁን አጣጥፎ በመቀመጡና የህዝቡን ንቃተ-ህሊና የሚያሳድግና ለተቃውሞ የሚነሳሳው ትችታዊ ሀተታ ለመስጠት ባለመቻሉ ነው።

በዚህ መልክ ከማዕድን ጀምሮ፣ ከህንፃ ስራ፣ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ስትራቴክ የሆኑ የእርሻ ጥሬ-ሀብቶች፣ እንደሲሚንቶና ስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ኩባንያዎች፣ የባንክ መስክና ሌሎችም ቁልፍ የሚባሉ  የንግድ መስኮች በህውሃትና በካድሬዎቹ እጅ የተያዙ ናቸው። በዚህም የተነሳ ማፊያዊ በሆነ የዘረፋ ስርዓት በመሰማራት ባጭር ጊዜ ቢሊዬነሮች ለመሆን በቅተዋል። ከአገር አልፈው ውጭ አገር ሁሉ ቤት ለመስራትና ሀብት ለማሽሽ ችለዋል።  በዚህ ዐይነቱ የምዝበራ ሂደት ውስጥ የሚተባበራቸውን በማቀፍና ሀብታም በማድረግ፣ የሚቃወማቸውን ወይም ደግሞ ይወዳደረኛል፣ ይቀናቀነኛል የሚሏቸውን በሙሉ በአንዳች ዐይነት ነገር ማስወገድ ችለዋል። ይሁንና ይህንን ሁሉ አደገኛ ድርጊት ፈጽመው፣ አገሪቱን ወደ ማያቋርጥ የርስ በርስ ጦርነት እንድታመራ መንገዱን ካመቻቹ በኋላ እስካሁን ስንሰራ የነበረው የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ነው ይሉናል። ህገ-መንግስቱና በዚህ ላይ የተመሰረተው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የብሄረሰብ ክልላዊ አስተዳደር ትክክል ነው ይሉናል። የኢትዮጵያ ህዝብም እንደ አንድ ህዝብ የሚጠራ ሳይሆን የተለያዩ ብሄረሰቦች አገር ነች እየተባለ ነው። ይህ ዐይነቱ በየቀኑ እንደዳዊት የሚደገም አባባል የግዴታ በየብሄረሰቡ ኤሊት ጭንቅላት ውስጥ እንዲቀረጽ ለመደረግ በቅቷል።

ህወሃት ከሞላ ጎደል ስልጣኑኑ ከለቀቀ ከሁለት ዓመት ተኩል ጀምሮ አይ መልሶ ለመምጣት፣ አሊያም ደግሞ እሱ በሚተማመንባቸው ሰዎች ስልጣንን ለማሲያዝ ሲል አገሪቱን በጦርነት ማመስ ጀመር። በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ሁኔታው በከፍተኛ  ደረጃ በመጧጧፍ በተለይም በአማራው ወገናችንና በኦርቶዶክስ ሃይማኖትና  ቀሳውስቱ ላይ እጅግ አሰቃሲ ድርጊት ፈጽሟል። በዚህ ፋሺሽታዊ ድርጊቱ የየብሄረሰቡ ክልል መሪዎች፣ በተለይም አንዳንድ የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪዎችና ኦነግ ሸኔ የሚባለው ቡድን በመተባበር እንዳየነው ሻሸመኔና ዝዋይ ላይ አሰቃቂ ድርትጊቶችን ፈጽመዋል። ሰሞኑን ደግሞ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማለት የሰሜን ዕዝ በሚባለው ክልሉንና አካባቢውን በሚጠብቀው የአገራችን ወታደር ላይ ሳይስበው ጦርነት ክፍተዋል። ሰሞኑኑ በዝርዝር የሚወጡት ማስረጃዎች በሙሉ የሚያረጋግጡት በአገሪቱ ምድር እዚህና እዚያ የሚኖሩ አንዳንድ የትግሬ ብሄረሰብ ተወላጆችና ከህውሃት ጋር በጥቅም የተያያዙ በመሳሪያ እንደታጠቁ ነው። ዋና ዓላማቸውም አጥፍቶ የማጥፋት ስትራቴጂ ነው። ይሁንና ግን ወደዚያ ሳይደርሱ ጨላማን ተገን በማድረግ መሳሪያዎችን ወደውጭ አውጥተው በየሜዳው ላይ ጥለዋቸዋል።

ይህንን ነገር ሁሉ ስንመለከት በዓለም ታሪክ ውስጥ አንድን አገር አስተዳድራለሁ የሚል አገዛዝ በእንደዚህ ዐይነት ማፊያዊ ተግባር የተሰማራበት አገር በፍጹም የለም። ስልጣኑኑም ከለቀቀ በኋላ ወደ ውንብድና ተግባር በመሰማራት የእርስ በርስ ጦርነት በመቀስቀስና እጠለዋለሁ የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል አሰቃቂ በሆነ መልክ የገደለ አገዛዝ ከወያኔ በስተቀር በሌላ አገርና አገዛዝ የተለመደ አይደለም፤ ታይቶም አይታወቅም። ይህንን ሁሉ ጉዳቸውን ስንመለከት የህውሃት ሰዎችና ካድሬዎቻቸው በዚህ ዐይነት የውንብድናና የግድያ ስራቸው እንወክለዋለን በሚሉት በትግራይ ብሄረሰብ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አንድም ደቂቃ ቆም በማለት የቅንጣትም ያህል በፍጹም አላሳቡም። ይሁንና ግን ሊነግሩን ሊያሳምኑን የሚፈልጉት የትግራይ ብሄረሰብ እንደጠላና በተለይም ደግሞ ባላፈው ሁለት ዓመት ተኩል አህዳዊ አገዛዝን ለመመለስ አ የፌዴራል አገዛዙ እንደሚሰራና ይህንንም መከላከል እንዳለበቻውና፣ ያላቸውም አማራጭ ከመዋጣቸው በፊት በፍጥነት በማትቃት ድልን  ተቀዳጅቶ ስልጣን ላይ እንደገና ቁጥጥ ማለት ነው። በ24.02 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጽሙ ያሰቡት በቀላሉ ሁሉን ነገር ተቆጣጠረን ስልጣን ላይ እንደገና ተመልሰን እንመጣለን የሚል ነበር። ይህ ቅዠታቸው ግን ሳይሳካ ቀረ። የኢትዮጵያ  ወታደርና የአማራ ሚሊሺያና ፋኖዎች ባሳዩት ትብብርና ቆራጥነት የተሞላበት ትግል አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜው ውስጥ ወሳኝ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደ  መቀለ በማምራት ላይ ናቸው። የህውሃት ወንበዴዎች በቀላሉ ሊያመልጡ የሚችሉበት መንገድ ሁሉ ተዘግቶባቸዋል። ያላቸው አማራጭ አይ እጃቸውን መስጠት፣ አሊያም ደግም ራሳቸውን ማጥፋት። ባጭሩ ከዚህ ሁሉ አስተሳሰብና ድርጊት የምንማረው ቀደም ብሎም ሆነ ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ፖለቲካ የሚባል ነገር ተግባራዊ የሆነበት ጊዜ የለም። የአገራችንም ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ፖለቲካ የሚባለው ነገር፣ በመርሆች ላይ፣ በርዕ ላይ፣ በሞራል ላይ፣ በስነ-ምግባር ላይ፣ በዕውቀት ላይ፣ በሀቀኝነት ላይና ህብረተሰርብአዊ ኃላፊነትን በመሰማት ላይ የተመረኮዘ፣ የተቀደሰ፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና መመሪያ መሆኑ ቀርቶ የውሸታሞችና የወንበዴዎች መሳሪያ የሆነበት ሁኔታ እንመለከታለን። ከዚህም በላይ ፖለቲካ በቂም በቀል ላይ የተመሰረተና  የእኔን አመለካከትና አስተሳሰብ ያልተከተለ ጠላቴ ነው ወደሚለው አገር አፍራሽ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ፖለቲካ ያገባኛል በሚሉና ይህንን ወይም ያኛውን ድርጅተ እከተላለሁ በሚሉ ካድሬዎች መንፈስ ላይ ሰርፆ የገባ አደገኛ አስተሳሰብ ለመሆን በቅቷል። ከዚህ ዐይነቱ አደገኛ አስተሳሰብ ካልተላቀቅንና ፖለቲካ በፍልስፍናና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የህብረተሰብ ችግር መፍቻና ታሪን መስሪያ መመሪያ መሆኑን እሳክለተገነዝብን ድረስ የህዝባችን የወደፊት ዕድል የጨለመ ይሆናል ማለት ነው።

መደምደሚያ!

ዛሬ አገራችን ከገባችበት አስቸጋሪ ሁኔታና በየአካባቢው ካሉ ኋላ-ቀር ከሆኑ የጎረቤት አገሮች አገር ሁኔታ ስንነሳ ከስሜትና በቀላሉ ከመወነጃጀል ባሻገር እንዴት አድርገን ነው የአገራችንን ሁኔታ የምናጤነው፣ የፖለቲካውንስ  ነገር በምን ዐይነት መነፅር ነው የምንመለከተውና ሳይንሳዊ ትንተናና አማራጭ መፍትሄ ማቅረብ የምንችለው? አንድ በሁላችንም መንፈስ የተቀረፀ ሳይንሳዊ ያልሆነ አመለካከት በመንፈሳችን ተቀርጿል። አገራችን ውስጥ ላለው ችግር ተጠያቂው ሰዎች ሳይሆኑ ህገ-መንግስቱና የህግ የበላይነት አለመኖር ነው የሚል ነው። በዚህ ዐይነቱ ተራ ሎጂክ እነዚህ ነገሮች በምንፈልጋቸው መንገድ መልክ ከያዙ ሁሉም ነገር ይስተካከላል የሚል ነው። ሌላው ደግሞ የህዝብ ተቀባይነት ያለው አገዛዝ ስልጣኑን መያዝ አለበት፤ ለዚህ ደግሞ ምርጫ መካሄድ አለበት የሚል ነው። ይሁንና ግን በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ግንዛቤ ያላገኘው ነገር በዓለም ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ አገሮች ወርቃማ የሚመስል ህገ-መንግስት ቢኖራቸውም ሆነ በየአራት ዓመቱ ምርጫ ቢካሄድም የአብዛኛው ህዝብ ኑሮ አሰቃቂና መሰደድ ነው። በአብዛኛዎች የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች፣ በየአራት ዓመቱ ምርጫ ቢካሄድም አገዛዞች የዘራፊነት ባህርይ ያላቸውና በጣም ጨቋኞች ናቸው።

ስለሆነም በአገራችን ምድር ያለው ህገ-መንግስት ቢቀየርና ምርጫም ቢካሄድም ተዓምር ሊፈጠር በፍጹ አይችልም። ከፖለቲካ ስሌት አንፃር 27 ዓመት ሲሰራበት የቆየን ህገ-መንግስትና የክልል አስተዳደር ዝም ብሎ የሚቀየር አይደለም። ይህ ከመሆኑ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ህገ-መንግስቱና የክልል ፖሊሲው ለዕድገትና ለሰላም ጠንቅ የሆኑበትን ምክንያት ማሳየት ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አማራጭ ማቅረብ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር እኛ እንደምናስበውና እንደምናልመው ሁኔታዎች እንደዚሁ ቀላል አይደሉም። በዚህ ላይ የዓለም ፖለቲካ ሁኔታና ግሎባል ካፒሊዝም በቀላሉ መፈናፈኛ  የሚሰጡ አይደሉም። ቆም ብለን ማሰብ አለብን ማለት ነው።

ከዚህ ስንነሳ በተጨባጭ የሚታየውን ሁኔታ እንዴት ነው የምንገመግመው? እንዴትስ ነው የምንመለከተው? የሚለውን መመርመር ያለብን ይመስለኛል። የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ድል በድል ከተቀዳጀ በኋላ በየአካባቢው የአገራችን ህዝብ ስሜት እንደገና ተነሳስቷል፤ አብዛኛው ህዝብ ፍቅርንና ሰላምን እንደሚፈልግ አረጋግጧል። በቆራጥነት ለሚታገለው ወታደራችንም የተቻለውን ያህል ዕርዳታ እያደረገ ነው። ኢትዮጵያዊነቱንና በጋራና ተባብሮ ለመኖር እንደሚፈልግ አረጋግጧል። ይህን ሁሉ ስንመለከት ፖለቲካውንና የራሳችንን ስሜት በአዲስ መልክ መመርመር ያለብን ይመስለኛል። ቀደም ብለው የተሰሩ ፖለቲካዊ ስህተቶችንና ወንጀሎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከስሜት የወጣ ወይም የፀዳ ፖለቲካ እንዴት ማካሄድ እንችላለን በሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን። ተከታታይነት የሚኖረው ፖለቲካና አስተማማኝ የሆነ የዕድገት ፖሊሲ እንዴትስ ነው መንደፍ የምንችለው በሚለው ላይ መወያየትና መከራከር አለብን። ዝም ብለን በጭፍን  ህገ-መንግስቱ መለወጥ አለበት፤ ምርጫም መካሄድ አለበት እያልን መጎትጎቱ ይህንን ያህልም ብዙ አያራምደንም። በምርጫም የአገራችን የተወሳሰበ ሁኔታ ይፈታል የሚል ዕምነት የለኝም። ሊኖር የሚችለው አማራጭ ቢያንስ አስር ዓመት ያህል አገሪቱን ሊያስተዳድር የሚችል በፍልስፍና፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሶስዮሎጂ፣ በኢንስቲቱሽናል ወይም በፊዚካል ኢኮኖሚክስ፣ በስነ-ልቦና፣ በአርክቴክቸርና በሌሎች ሙያዎች የሰለጠኑ መምህራን ቢያስተዳድሩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታና በፓርቲ ስም የሚንቀሳቀስቱን ብቃትነት በምመረምርበት ጊዜ አብዛኛዎች ድርጅት አለን የሚሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ፊዩዳላዊ ወይም ኋላ-ቀር የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው። በሌላ አነጋገር አገራችንን ወደ ዘመናዊነትና ወደ ስልጣኔ የመምራት ብቃትነት የላቸውም።  መልካም ግንዛቤ !!

                                                                                     fekadubekele@gmx.de