[gtranslate]

የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም !  ህግ የሰውን ልጅ መብት ማስከበሪያና ነፃነቱን ማረጋገጫ ነው !

                                                            

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                             የካቲት 28 2019

መግቢያ !

የህግ የበላይነት የሚባል በአገራችን የተለመደ አነጋገር ከየት እንደመጣ አይታውቀም የግራም ሆነ የቀኝ ፖለቲካን አራምዳለሁ የሚለውና፣ እንዲሁም አገር ወዳድ ነኝ ብሎ ድምጹን የሚያስተጋባው ሁሉ ስለህግ የበላይነት ሲጽፍና ሲያወራ ይሰማል። ይሁንና ግን ዘ ሩል ኦፍ ሎው(The Rule of Law) የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ቃል በቃል ሲተረጎም የህግ የበላይነት የሚለውን አይሰጠንም። ያም ሆነ ይህ በአገራችን ምድር ስለህግ የበላይነት መከበር ሲወራ ህግ ከሰው ልጅ በላይ እንደሆነ ተደርጎ ትርጓሜ ስለሚሰጠው በሰዎች እጅ የተጻፈ ግን ደግሞ ህይወት የሌለው ጽንሰ-ሃሳብ በእግዚአብሄር አምሳል ከተፈጠረው ሰው በላይ ሆኖ በመቆጠር የደሃው ህዝባችን መብት ይገፈፋል፤ ይደበደባል፤ ከቀየው እንዲፈናቀል ይደረጋል፤ እንዲያም ሲል ይገደላል። ወያኔ የሚባለው ከትግራይ የተውጣጣ የፋሽሺስትና የማፊያ ቡድን እንደዚሁ ለሰው ልጅ መብት መከበርና እንደመመሪያ የተጻፈውን ህገ-መንግስት ከህዝባችን ህይወት በላይ አድርጎ በመቁጠር በዕድገት ስም የህዝባችንን ሀብት ሲዘርፍ፣ ቤቱን ሲያፈርስና ወደ ቦይ ውስጥ እንዲጣል በማድረግ የጅብ እራት እንዳደረገው ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ እንደዚሁ ዘመኑ የእኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ እንችላለን፤ ቂም-በቀልም የመወጣት መብት አለን ብለው በስሜት በተነሳሱ ግን ደግሞ የታሪክና የህብረተሰብ ዕድገት ግንዛቤ በሌላቸው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎች በኗሪው ወገናችን ላይ በህግ የበላይነት ስም አሳበው ግፍ እየፈጸሙባቸው ስናይ በአገራችን ምድር የሰው ልጅ ህይወት የቱን ያህል እንደረከሰና እንደተናቀ መገንዘብ እንችላለን። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻቸን ቤታቸው በግሬደር ፈራረሶ ሜዳ ላይ ከእነልጆቻቸው ተጥለውና ሲያለቅሱ ስናይ ስልጣን የጨበጠው አዲሱ ትውልድ በየቀኑ አረመኔ እየሆነ እንደመጣ ማየት ችለናል። ስልጣንና ሀብት የቱን ያህል የአንዳንዶችን ልብ እንደሚያደልብና መንፈሳቸውን ሰልቦ አረመኔ እንደሚያደርጋቸው ያለፈው 27 ዓመት የአገራችን ታሪክ አረጋግጦልናል። ወያኔ ከስልጣኑ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተወግዶ በዶ/ር አቢይ ሲተካና እሳቸውም የሁላችንን ልብ የሚስብ ንግግር ሲያደርጉ ስንሰማና ሲስቁ ስናይ ለአገራችንና ለህዝባችን ብርሃን መጣላቸው ብለን ፈንድቀን ነበር። አገራችንና ህዝባችን ዲሞክራሲን እየተለማመዱና ተግባራዊ እያደረጉ በስልጣኔ ፋና በመጓዝ ለመጭው ትውልድ የምትሆን በጠንካራ መሰረት ላይ የምትገነባ አገር  ማስተላለፍ ይችላሉ ብለን ገምተን ነበር። ይሁንና ግን ይህ ፍንደቃና የልብ ደስታችን በሌሎች ጽንፈኞችና፣ ህግና መብት ምን እንደሆነ ማገናዘብ በማይችሉ የአንዳንድ የከተማ ወይም የክልል መሪዎች እየተጣሰ ነው። ታሪክ እራሷን የምትደግም ትመስላለች። በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ! መቼስ ነው የህዝባችን ሰቆቃ የሚያቆመው ? መቼስ ነው እፎይ ብሎ አርፎ የሚተኛው ?

ለመሆኑ የህግ የበላይነት የሚባል ነገር አለ ወይ ?

ዘ ሩል ኦፍ ሎው (The Rule of Law) የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ በማዕከለኛው አውሮፓ ዘመን በዚያን ጊዜ የፍጹም ነገስታቶችና የመሬት ከበርቴዎች በአርሶ አደሩ ላይ የፈለጋቸውን ነገር ያደርጉ ስለነበርና፣ በዚህም የተነሳ በአንዳንድ ቦታዎች መብቱ የተገፈፈው አርሶ አደር ለመብቱ ትግል ሲያደርግ የተመለከቱና የተመራመሩ የእንግሊዝ ሊህቃን አንድ ህብረተሰብ በዚህ ዐይነት ስርዓተ-አልባ ሁኔታ እንደማህበረሰብ ሊኖርና ኑሮውንም ለማሻሻል እንደማይችል በመረዳት የህግ ስርዓት መከበር እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። ይህም ማለት ማንኛውም ዜጋ በአምላክ ምስል የተፈጠረ በመሆኑ የመንግስታት ኃላፊነትና ግዴታ የማንኛውንም ዜጋ መብት ማስከበር ነው። በዚህ ዐይነቱ የመብትን ማወቅ ሂደት ውስጥ የግል ሀብት ወሳኝ ሚናን ቢጫወትምና፣ የግል ሀብት መኖር እንደፈጥሮአዊ ነገር ተቆጥሮ ቢወሰድም መንግስትም ሆነ ህግ ከማንኛውም ዜጋ በላይ ሊሆኑ እንደማይችሉ በተለይም ሚልተን የተባለው ዘ ፓራዳይዝ ሎስት በሚለው መጽሀፉ ውስጥ በደንብ አስቀምጦታል። በእሱ ዕምነትም ማንኛውም አገዛዝም ሆነ እራሱ ንጉስም ቢሆን የህዝብ አለኝታና  መብቱን የሚያስከብሩ እንደመሆናቸው መጠን የፈለጋቸውን ነገር ማድረግ አይችሉም። የህዝብን መብት የሚጥስና በሆነው ባልሆነው ነገር የሚያሰቃይ አገዛዝና ንጉስ መቀጣት እንዳለበት ለሚልተን ግልጽ ነበር። አንድን አገር የሚገዛ ንጉስ በልዩ ጥንቃቄ የተሰራና እንዲገዛ በእግዚአብሄር የተላከ ሳይሆን የኃይል አሰላለፍ ውጤት እንደመሆኑ መጠን ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ የህዝን መብት መግፈፍ ወይም መግደል አይችልም። ሀብቱንም የመንጠቅ መብት የለውም።  ስለሆነም ይላሉ አንዳንድ የሬናሳንስ ፈላስፋዎች የአንድ ንጉስና አገዛዝ ዋና ተግባር ለሚያስተዳድረው ህዝብ ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን መስራትና በስርዓትና በዲሲፕሊን እንዲኖር ማድረግ እንጂ ማሰቃየትና ማዋከብ አይደለም ተግባሩ። ለዚህ ነው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ዲስፖቲያዊ አገዛዞችን ጥሎ ሪፑብሊካዊ አገዛዝን ለመመስረት የማያቋርጥ ትግል የተካሄደው። የትግሉም መሳሪያዎች፣ ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ስነ-ጽሁፍናና ሌሎች ዕውቀቶች ሲሆኑ፣ ዋና ዓላማውም የጠራ የሃሳብ የበላይነትን በመቀዳጀት የአንድ አገርና ህብረተሰብ መመሪያ ኃይል ሳይሆን ዕውቀት፣ ህግ፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶችና እኩልነት በመከበር ማንኛውም ዜጋ በህግ ፊት እኩል መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።

በጊዜው ይህ ዐይነቱ በእነ ጆን ሎክና ሆበስ እንዲሁም በሚልተንና የኋላ ኋላ ደግሞ በእነ አዳም ስሚዝ ከገበያ ኢኮኖሚና ከሀበት ክምችት ጋር እያደገና እየዳበረ የመጣው አስተሳሰብ በጊዜው የከበርቴውን የበላይነት የሚያንፀባርቅና ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በፊዩዳሉ ስርዓት ላይ ድልን መቀዳጀቱን የሚያበስር ሁኔታ ነበር። የአውሮፓው ማህበረሰብ በካቶሊክ የወግ አጥብቅ ሃይማኖት መሪዎችና በመሬት ከበርቴው መደብ መሰቃየቱ ማቆም እንዳለበትና ዘመኑም የብርሃንና(Enlightenment) የሃሳብ የበላይነት ዘመን የታወጀበት ጊዜ ነበር። በዚህ ዐይነቱ ዕልክ አስጨራሽና የኋላ-ቀር ኃይሎችን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አስወግዶ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተገነባ አገር መመስረቱ የጊዜው አዋጅ በመሆን ይህ ዐይነቱ የነፃነት ብርሃንና እየዳበረ የመጣው ዕውቀት በተለያየ ፍጥነት የብዙ አውሮፓ አገሮችን ቀስ በቀስ በማዳረስ ለኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት ጣለ። በዚህም አማካይነት ጥበብና ክላሲካል ሙዚቃ እንዲሁም ስነ-ጽሁፍ(Literature)  ሲያብቡ፣ እያንዳንዱ ግለሰብም ዕውነተኛ ነፃነት የማግኘት ዕድል አጋጠመው። ቀስ ቀስ እያለም የማቴሬያል ሁኔታዎች ሲሻሻሉና በአገር ደረጃም የባቡር ሃዲድ ሲዘረጋ ማንኛውም ዜጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመዘዋወር ኑሮውን ማሸነፍ እንደሚችል በመረዳት በግለሰብ ታታሪነትና በመንግስት ጣልቃ-ገብነት አዲስ የኢኮኖሚ ስርዓትና ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትና እሴት በመፈጠር ህዝቡን ማዳረስ ቻለ። ህብረተሰቡም በጎሳ የተከፋፈለና በተለያየ ቋንቋ በመነጋገር የማይግባባ ሳይሆን፣ አንድ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ በመዳበርና ተቀባይነት በማግኘት ህብረተሰብአዊ  ዕድገትን ማምጣት ተቻለ። ማንኛውም ሰው የዚህ ወይም የዚያኛው ጎሳ አባል ሆኖ የሚታይ ሳይሆን የዚህ ወይም የዚያኛው መደብ አባል በመሆን መብቱን እንደዜጋ የሚያስከብር ሆኖ ተሰማው። በስራ ቦታ የሚደርስበትን በደልና የደሞዝ ጥያቄዎች የመሳሰሉትን ጉዳዮች ማንሳትም የሚችለውና የሚከራከረው በሙያ ማህበር በመደራጀትና በድርጅቱ አማካይነት ሊሆን ቻለ። በዚህም አማካይነት ከስርዓተ-አልባ ሁኔታ ይልቅ በድርጅት መደራጀትና ህግንና ስርዓትን አክብሮ ለመብት መታገልና፣ እንዲሁም ማንኛውም የመንግስት አካል የግለሰብን መብት ሳይጥስ ማንኛውንም ዜጋ እንደ እኩል ዜጋ በማየት ማሰተናገድና ጥያቄውን ለመመለስ መቻል ተቀባይነት ያገኘ የአሰራር ስልት ከደም ጋር በመዋሃድ ለፈጠራና ለኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታ ተፈጠረ።

ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ በአውሮፓ የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ውስጥ የህግ ስርዓት መኖርና መከበር አለበት ብለው በተነሱና በሰበኩ የአውሮፓው ምሁራን ዘንድ ህግ ከሰዎች በላይ በመሆን ስልጣንን በአጋጣሚም ሆነ በምርጫ የያዘ አገዛዝ ወይም ግለሰብ እያንዳንዱን ዜጋ እንደፈለገው ሊያሽከረክር ይችላል ብለው ያስተማሩበት ጊዜና ቦታ የለም። ህግም የሚጣስ ከሆነ እንደየሁኔታው ከህግ አንፃር በማጣራት ሚዛናዊ ፍርድና እርምጃ የሚወሰድ እንጂ ዝም ብሎ የህግ የበላይነት ተጥሷል ተብሎ በደካማ ዜጋ ላይ የሚጣል የዱብ ዕዳ የለም። ፅንሰ-ሃሳቡም ቃል በቃል ሲተረጎም የህግ የበላይነት የሚል ሳይሆን፣ ዘ ሩል ኦፍ ሎው ማለት የህግ ስርዓት መከበር አለበት፤ ማንኛውም ዜጋ መብቱንና ግዴታውን ይወቅ ማለት እንጂ፣ የህግ ተገዢ በመሆን እየተሸማቀቀ ይኑር ማለት አይደለም። ይሁንና ግን እንደነዚህ የመሳሰሉ ፅንሰ-ሃሳቦች ከትርጉማቸው እየተዛነፉና ሌላ ትርጉም እየተሰጣቸው አንዳንድ የበላይነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎችና አገዛዞች የሰውን መብት የሚጥሱበትና፣  አንዳንዶች ደግሞ ጠብመንጃ በማንገት ተራውን ህዝብ የሚያስፈራሩበትና እንዲያም ሲል የሚገድሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአገራችን ምድር የተስፋፋው ጥራዝ ነጠቅነትና የህብረተሰብን አገነባብ ታሪክ ያላገናዘበ አተረጓጎም -ለምሳሌ የማንነት ጥያቄ ወይም ደግሞ አዲስ አበባ ድሮ ፍንፍኔ ተብላ ነበር የምትጠራው- እያሉ ማውራትና ማስፈራራት ሰፊው ህዝብ ተንሳፎና ተሳቆ እንዲኖር የሚያደርገው አደገኛ የጥራዝ ነጠቆችና የወጣት ፈሽሽቶች ዘመቻ ነው። ረጋ ብሎ እያሰበ እንዳይሰራና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዳይፈጥር የሚያግደው አደገኛ የስነ-ልቦና ጦርነት ነው። ህብረተሰብአዊ ውዝግብ እንዲፈጠር የሚያደርግና የውጭ ኃይሎች በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ሰተት ብለው በመግባት የአገራችንን ዕድል እንዲወስኑ በር ከፍቶ የሚሰጥ አደገኛ ጨዋታ ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ጥራዝ-ነጠቅነትና አምባገነንነት ወይም የጥቂቱ ንዑስ ከበርቴ ፋሺሽታዊ ድርጊት እልባት እስካላገኘ ድረስ ከፍተኛ የሆነ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ መፈጠሩ የማይቀር ጉዳይ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ዛሬ እጠቀማለሁ፣ የበላይነትንም በመቀዳጀት የህዝባችንን ዕድል እንደፈለጉት አሽከረክራለሁ የሚለው ኃይል እራሱም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገባና እወክለዋለሁ የሚለውን ብሄረሰብ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከተው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ብርሃንና ስልጣኔን የሚያመጣለት ሳይሆን የዝንተ-ዓለሙን በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚያደርገው አደገኛ አካሄድ ነው።

የለገጣፎና የለገዳዲ ጉዳይ ! ሀዝብን የማፈናቀሉ ሁኔታ !

እንደሚታወቀው በእነዚህ ከተማዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ ከብዙ መቶ ዐመታት ጀምሮ  ህዝብን በስርዓት የሚያስተዳድር የሰለጠነ ተቋማት ስላልነበርና ስለሌለ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ቤቱን ወይም ጎጆውን ካለዕቅድና ካለስርዓት ነው ይሰራ የነበረው። ይህ ደግሞ የሰፊው ህዝብ ችግር ሳይሆን በየዘመኑ የሚነሳ ምሁር ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በማድረግና ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊናው ዳብሮ ሰፊው ህዝብ የሰለጠነ ኑሮ እንዲኖር  የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማድረግ ባለመቻሉ ነው። የኢትዮጵያን የምሁር እንቅስቃሴ ታሪክ ገረፍ ገረፍ አድርጎ ለተመለከተ መገንዘብ የሚቻለው አገርንና ህብረተሰብን የሚመለከት በሳይንስና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለማዳበር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ እራሱ ምሁሩ አንድ አገርና ህብረተሰብ በምን ዐይነት መሰረት ላይ ቢቆም ነው ተከታታይነት ሊኖረው የሚችለው በሚለው ላይ ውይይት እንዳይደረግ ከመጀመሪያውኑ መንገዱን ስለሚዘጋ ነው። በመሆኑም ብቻውን የሚንቀሳቀሰውና የሚኖረው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እያረሰ ከማብላት በስተቀር ኢትዮጵያ እየተባለ ከሚጮህላት አገር ምንም ያተረፈው ነገር የለም። የህዝቡም ኑሮ ከደሳሳ ጎጆና የቆርቆሮ ቤቶች ኑሮ ያላለፈና ኃይለኛ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ለአደጋ ተጋልጦ የሚኖር ነው። በአንፃሩ የአውሮፓውን የከተማ አገነባብ ታሪክ ስንመለከት፣ በተለይም ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተካሄደውን የከተማ አገነባብ ታሪክ ለተመለከተ በብዙ ምርምርና ጥናት በዕቅድ ከተማዎች እንደተቆረቆሩና ቤቶችም እንደተገነቡ መገንዘብ እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና የነበራቸው ምሁራንና ሳይንቲስቶች ከራሳቸው ህይወት ይልቅ የአገርንና የህዝብን ጉዳይ አስቀድመው በማየታቸውና ሳይታክቱ በመስራታቸው ውብ ውብ ከተማዎችን ገንብተው አልፈዋል። ስለሆነም በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ያደገ አዳዲስ ትውልድ የህንፃ አሰራር ተቋማት በመክፍትና በመመራመር በቁጥር እየጨመረ ለሚመጣው ህዝብ ቤቶች በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ተሰርቶ ሊቀርብ የሚችልበትን ሁኔታ ማጥናትና ተግባራዊም በማድረግ ህብረተሰቡ የተስተካከለ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ችሏል። እኛም ከአገራችን ወጥተን በየአገሩ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የዚህ ዐይነቱ የሰለጠኑ ኑሮ ተካፋይ በመሆን አነሰም በዛም ደልቶን እንኖራለን። በደንብ የተጠና ከተማና የቤቶችና የህንፃዎች አሰራር እንደባህል በመወሰዱ ማንኛውም ዜጋ ህብረተሰቡን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ነገሮች እንዳይሰራ ይቆጠባል። ግለሰቦችም ቤት ለመስራት በሚፈልጉበት ጊዜ አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥናት በአርክቴክቸሮች አማካይነት እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ ቤት የመስራት ፈቃድ ይሰጣቸዋል። መሬትም በማጭበርበር አንዱ ለሌላው የሚሸጠው ሳይሆን አንድ ቤት ከመሰራቱ በፊት ቤት ለመስራት የሚፈልገው ሰው መሬቱ የራሱ ለመሆኑ የሚያረጋግጥ ካርታ ማቅረብ አለበት።

ወደ አገራችን፣ በተለይም ደግሞ ወደ ለገጣፎና ለገዳዲ ስንመጣ ችግሩን የፈጠሩት ራሳቸው ቤት ሰርተው መኖር የጀመሩትና፣ ቤታቸው እንዲፈራርስ የተደረገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ፣ ዋናው ተጠያቂዎች በየአካባቢው ያሉትና አካባቢውን የሚያስተዳድሩት አንዳንድ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ በአሁኑ አጠራር ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ካድሬዎች ናቸው። አንዳንድ ካድሬዎች ስልጥናቸውን በመጠቀም  መሬት ለመከራየት ወይም ለመግዛት ለሚፈልግ ሰው መሬትን በብዙ ሺህ ገንዘብ በመሸጥና ቤት እንዲሰራበት በማድረግ ቤት ካለዕቅድ እንደተሰራ ይታወቃል። በሌላ አነጋገር ለዚህ ዐይነቱ ዕቅደ-አልባ የቤት አሰረራ ተጠያቂዎቹ ራሳቸው በብዙ ሺህ ገንዘብ አውጥተው መሬት ተመርተውና ሰርተው የሚኖሩት ሰዎች ሳይሆኑ የከተማዎቹ አስተዳዳሪዎች ናቸው። ይህ መሆኑ እየታወቀ የተሰሩት ቤቶች ከህግ ውጭ የተሰሩ ናቸው እያሉ ቤቶችን ማፍረስና ኗሪውን ሰው ከእነልጆቹ በየሜዳው እንዲጣል ማድረግ ምን ዐይነት ፈሊጥ ነው ?

ለማንኛውም አንድ የከተማ ከንቲባና አስተዳደሩ በማንአለኝበት አፍራሽ ሰዎች ልኮ ቤቶች በግሬደር እንዲፈራርሱ ከማድረጉ በፊት ቤቶች በምን ዐይነት ሁኔታ፣ በማንስ ፈቃድ እንደተሰሩና፣ መሬቱንም እንዴት ለመከራየትም ሆነ ለመግዛት እንደቻሉ ሰፊ ጥናት ማካሄድ ይኖርበታል። ቤቶች ካለዕቅድ ነው የተሰሩት ከተባለና ከተማዎቹ አዲስ ዕቅድ ያስፈልጋቸዋል የሚባል ከሆነ ደግሞ ነገሩን ለሚመለከታቸው ኗሪዎች ካስረዱ በኋላ ቤቶች በአዲስ መልከ ተሰርተው እስኪያልቁ ድረስ የሚኖሩበት አማራጭ ቤቶች እንዲሰጣቸው ያስፈልጋል። የለም ይህንን ዐይነቱን ጤናማና ሰብአዊ አሰራር በፍጹም ሰምተን አናውቅም፣ ባህላችንም አይደለም የሚባል ከሆነ ደግሞ የግዴታ አዋቂዎች ጋር ሄዶ ምክር መጠየቅና፣ ይህ ዐይነቱ ችግር በምን መልክ ሊወገድ እንደሚችል ግንዛቤ በመውሰድ ችግሩ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልክ ሊፈታ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እጅግ አስፈላጊ ነው። እስከሚገባኝ ድረስ የየክልሉና የከተማዎች አስተዳዳሪዎች በመሰረቱ የሰው ልጅና ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆኑ እስከዚህም ድረስ የገባቸው አይመስለኝም። ለም መሬቶችን ለሆላንድ የአበባ ኩባንያዎች በማከራየትና አበባ እንዲተከልባቸው በማድረግ አካባቢ እንዲመረዝና የሰራተኛውም ጤንነት እንዲቃወስ ከሚያደርጉ ሰዎች ብዙም ነገር የሚጠበቅ ያለ አይመስለኝም። ገንዘብ እየነጠቁ ራሳቸውን ከማደለብ በስተቀር፣ ለምን እንደሚኖሩና ወዴትስ እንደሚያመሩና ዓላማቸውም ምን እንደሆነ የተገነዘቡ ባለመሆናቸውና ራሳቸውንም ለመጠየቅ ስለማይችሉ ቤቶችን በማፈራረስ ወላጆች ከእነልጆቻቸው በየቦታው ተበትነው እንዲወድቁ ማድረጉ ይህን ያህልም ሊያስደንቀን አይገባም። የሚያሳዝነው ነገር ግን በነፃነትና ራስን በራስ ማስተዳደር ስም እንደዚህ ዐይነት ወንጀል ሲፈጸም ሲታይና የአገርና የህዝብ ዕድገት ለብዙ መቶ ዐመታት እንዲተጓጎል መደረጉ ነው።

ከዚህ ዐይነቱ አሳዝኝ ታሪክ ስንነሳ ራሱን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ብሎ የሰየመው የጎሳ ድርጅት የዲሞክራሲ መሰረተ-ሃሳቦችን ተረድቶ እንደሆን እንድንጠራጠር ያስገድደናል። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ የጎሳ ድርጅት ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። ምክንያቱም የዲሞክራሲ መብት ጉዳይ የአንድን አገር ህዝብ መብት የሚመለከትና የማህበራዊ ጥያቄዎችን የሚያካትት በመሆኑ በሂደት ውስጥ የሚዳብርና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጠቃልል ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ አንድ ድርጅት በፓርቲ ደረጃ ተደራጅቻለሁ የሚልና ዲሞክራሲ የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ የሚያንጠለጥል ከሆነ በድርጅቱ ውስጥ ጥናትና ክርክር መካሄድ አለባቸው። በሶስተኛ ደረጃ፣ አንድ በዲሞክራሲያዊ መርሆች ላይ የተመሰረተ ድርጅት በውስጡ አንድን ህብረተሰብ የሚመለከቱ፣ እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የማህበራዊ ጉዳዮች፣ የቤት ስራና የከተማ አገነባብ ጉዳይ፣ የኢንዱስትሪ ተከላና የስራ ቦታ መፍጠርን ጉዳይ፣ የጤንነት ፖሊሲንና የባህል መዳበርንና የባህል ማዕከሎችን የመስራት ጉዳይ… ወዘተ. በስራ ክፍፍል በተደራጁት አባሎች ውስጥ  በማጥናትና በመወያየት አጠቃላይ ፖሊሲ ማውጣት የሚችል መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ በአንድ ድርጅት ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብና የአሰራር ስልት ሊዳብሩ ይችላሉ። እያንዳንዱ የድርጅቱ አባልም የጭንቅላት ነፃነት በማግኘት ሃሳቡን ወደ ውጭ አውጥቶ ከማንኛውም ዜጋ ጋር የመነጋገርና የማስረዳት፣ እንዲሁም የመከራክር ድፍረትን ያገኛል። ድንፋታንና ቁጣን ከማስቀደም ይልቅ ቀስ በቀስ ዲሞክራሲያዊ ክርክርን፣ ጥያቄን መጠየቅና ለመጠየቅም፣ እንዲሁም ሎጂካዊ በሆነ መልክ መልስ ለመስጠት የሚችል ፈታ ያለ ጭንቅላት ይኖረዋል።  እንደምከታተለው ከሆነ በኦዴፓም ሆነ በተለያዩ በብሄረሰብ ደረጃ በተደራጁ የአገራችን የክልል አስተዳዳሪዎች ውስጥ ይህ ዐይነቱ ጥናትና የአሰራር ልምድ ስለማይታወቅ በማንነት ጥያቄ  ስም ወደ አደገኛ ሁኔታ በመጓዝ ህብረተሰብአዊ ትርምስ እንዲፈጠርና አገራችንም ለብዙ መቶ ዐመታት ወደ ኋላ ቀርታ እንድትኖር ሳያውቁት ሁኔታዎችን እያመቻቹ ነው። የየድርጅቶች መሪዎችም ሆነ ካድሬዎች የበላይነት ስሜት የሚሰማቸውና ሰፊውን ህዝብ የሚንቁ እንጂ ህብረተሰብአዊ ችግሮችን ለመፍታትና ታላቅ አገር ለመገንባት የተዘጋጁ እንዳልሆኑ ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ተከታታይነት ወደሚኖረው አምባገነናዊ ስርዓት በመለወጥና ስር በመስደድ አገራችን ዕውነተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ተሃድሶ እንዳትጎናጸፈ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ አደገኛ ሁኔታ ለመላቀቅ የግዴታ ሁለ-ገብ የሆነ ጭንቅላትን የሚያድስና ዕውነተኛ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ ሁለ-ገብ ዕውቀት መስፋፋትና በግልጽ የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ሰፊው ህዝብ መደራጀትና በስራ ላይ መሰማራት አለበት። የአንድ አገር ችግር በጥቃቅን ፕሮጀክቶችና ከውጭ አገር በሚመጣ ብድርና ዕርዳታ መፈታት እንዳማይችል ተገንዝቦ ራስን መቻል የሚለውን መርሆ በማስቀደም አገርን ለመገንባት ታጥቆ መነሳት ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ በግልጽ መታወቅ ያለበት ነገር ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣና ተከልሎ የሚኖር ጎሳ በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በፍጹም ሊያድግ አይችልም። የስልጣኔና የህብረተሰብን ዕድገት ታሪክ ላጠናና ለተከታታለ አንድ አገር ሊያድግና ህዝቡም ንቃተ-ህሊናው  ሊጎለምስ የሚችለው የተለያዩ ሃሳቦች ከውጭ መጥተው አገር ውስጥ ካለው ጋር ሲቀላቀሉና ሲዋሃዱ ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካን ጎልቶ የሚታይ ነው። ምዕራብ አውሮፓ ከግሪክ በመጣ ሳይንስና ፍልስፍና አማካይነት ነው ከጨለማው ዘመን በመላቀቅ ቀስ በቀስ የስልጣኔን ብርሃንን ማየት የቻለውና በቴክኖሎጂ ያደገው። ከዚህም በላይ በየአንዳንዱ የምዕራብ አውሮፓ አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ዕድገት ሊመጣ የቻለው ከሌላ ቦታ ፈልሰው የመጡ ህዝቦች ከአገሬው ህዝብ ጋር በመጋባትና በመዋለዳቸው ነው። አሜሪካም እንደዚሁ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው ከውጭ በመጣ ዕውቀት አማካይነት ነው። ዛሬም ቢሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከየአገሩ በመምጣትና እዚያው በመኖር የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል ለመሆን ችለዋል። እዚህ እኛ የምንኖርበት በርሊን ከተማ ብቻ ከ150 አገሮች የመጡ ሰዎች በመኖር ለኢኮኖሚው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን የባህል ዕምርታን ሰጥተውታል። የኢጣሊያን፣ የቱርክ፣ የስፔይን፣ የኢትዮጵያና የሌሎች አገሮች የምግብ ቤቶች በብዛት ይገኛሉ። በመንግስት መስሪያቤትም ሆነ በግል ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ አገር ሰዎች ይገኛሉ። አብዛኛዎችም የመምረጥና የመመረጥ መብትና ዕድል አላቸው። ከዚህ ስንነሳ ከተማን ከተማ የሚያደርገው የተለያየ ህዝብና የተለያየ ባህል ሲኖሩና ሲዳብሩ ብቻ ነው። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ሲቪክ ማህበረሰብ ሊዳብርና ተከታታይነት የሚኖረው ስራ ሊሰራ የምችለው። በአንፃሩ በዚህ መልክ የማይደራጅና የማይታቀድ ከተማ የድንቁርናና የድህነት ሰለባ ይሆናል። ይህንን ነው የለገጣፎና የለገዳዲ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን የሚመኙት። ብርሃንን ሳይሆን ጨለማን ነው የሚሹትና እየተደናበሩ ወደ ገደል ለመግባት የሚፈልጉት።

ሰለሆነም ከእንደዚህ ዐይነቱ ያልሰለጠነ አሰራርና አስተዳደር መላቀቁ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የማንነት መብት ወይም ራስን በራስ ማስተዳደር በሚል ሰበብ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ህዝብ በጥቂት ዘመናዊ ካድሬዎች መረበሽና ፍዳውን ማየት አይገባውም። መታወቅ ያለበትም ጉዳይ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የሁሉም ዜጋ እንደመሆኗ መጠን እያንዳንዱ ዜጋ የፈለገበት ክፍለ-ሀገር ወይም ክልል ሄዶ የመስራትና ሀብት የማፍራት፣ እንዲሁም በአስተዳደር  ውስጥ የመሳተፍ መብት አለው። ማንኛውም የየክፍለ-ሀገሩ አስተዳደር ወይም መስሪያቤት ለሁሉም ዜጋ ክፍት መሆን አለበት። ፖሊሶችም ከሁሉም ብሄረሰብ በመውጣጣት ፀጥታን የሚያስከብሩ መሆን ያለባቸው እንጂ ከአንድ ጎሳ በመመልመል ብቻ ሌላውን ጎሳ የሚያምሱበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም። በመሆኑም ስለለውጥ በሚወራበት ጊዜ እነዚህ ሁሉ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ በተረፈ ግን የተራው ህዝብ ቤቶች ካለአግባብ እንዲፈርሱና ሰዎችም በየቦታው እንዲጣሉ ያደረጉ የከተማዎቹ ከንቲባዎችና የአስተዳደር አባላት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። በህግ የበላይነት ስም በማሳበብ እንደዚህ ዐይነት ወንጀል ሰርተው እጃቸውን አጣጥፈው ሊቀመጡ በፍጹም አይገባቸውም። ይህ ብቻ ሳይሆን ቤታቸው የፈረሰባቸው ካሳ ማግኘት አለባቸው። ቤት ተሰርቶ እንዲሰጣቸው የክልሉ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን መንግስትም አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለበት። ከዚህ በተረፈ እንደዚህ ዐይነት ነገር ወደፊት እንዳይደገምና የሰፊው ህዝብ መብት እንዳይጣስ በአስተዳደር ውስጥ ተቀጥረው ለመስራት የሚፈልጉ ወደ ተግባር የሚመነዘርና በየአካባቢው ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥር የሚችል ዕውቀት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። የህዝብ አገልጋይ ለመሆን ብቃት ይኖራቸው እንደሆን ልዩ ዐይነት የጭንቅላት ምርምር ፈተናዎችን ማለፍ አለባቸው። ዕውነተኛ የህዝብ አገልጋዮች ለመሆን የተዘጋጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።  መልካም ግንዛቤ!  

fekadubekele@gmx.de