[gtranslate]

ኮረና ቫይረስና ሁለት ጎን ተፅዕኖው!!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ሚያዚያ 15፣ 2020

መግቢያ

በታህሳስ ወር 2019 ዓ.ም ሁዋን በሚባለው የብዙ ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የቻይና ከተማ የተከሰተውና በጉሮሮ አልፎ ሳምባን የሚጎዳና ወደ ሞትም ሊያደርስ የሚችለው ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ 19 በመባል የሚታወቀው አደገኛ ቫይረስ የዓለምን ህዝብ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ከቶቶ ከጤንነት መቃወስ አልፎ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። ይህ ኮረና ቫይረስ በመባል የሚታወቀው በ2003 ዓ.ም እንደዚሁ በቻይና ምድር ከተከሰተው ሳርስ ከሚባለው ቫይረስ ጋር ዝምድና ቢኖረውም፣ ኮቪድ 19 በመባል የሚታወቀው ይህ አዲስ ቫይረስ ቀደም ብለው ከተከሰቱት እንደ ሳርስ ከመሳሰሉት የኮረና ዘመዶች ጋር ሲነፃፀር በዐይነት የተለየና በጣምም አደገኛ እንደሆነ ሊደረስበት ተችሏል። ይህንን በመረዳት በሁዋን ከተማ የሚገኘው የዓለም የጤንነት ድርጅት ቅርንጫፍ(WHO) መረጃዉ ከደረሰውና ብዙ ሰዎችንም እያጠቃ ሲመጣ በጥር ወር 2020 ዓ.ም ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ሊኖረው የሚችል አደገኛ ቫይረስ ነው በሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳል። ይኸው የጤና ጥበቃ ድርጅት በጥር ወር 30፣ 2020 ዓ.ም ዓለምን ሊያዳርስ የሚችል የወረርሽኝ(Pandemic) በሽታ ነው በማለት ለመንግስታት ያስታውቃል።

ስለቫይረሱ ምንጭና መራባት የተለያዩ ትንታኔዎች(Theories) ይሰጣሉ። አብዛኛዎች ተመራማሪዎች የኮቪድ 19ኝን መነሻ የሌሊት ወፍ ናት ብለው ሲናገሩ፣ አንዳንዶች ደግሞ በእግሮቿ የምትንቀሳቀስ፣ ሰውነቷ እንደቀበቶ የተተለተለ(Armadillo) ለየት ያለች እንስሳ የቫይረሱ ምንጭ መሆኗን ይናገራሉ። ከዚህ ለየት ያለ አስተያየት ያላቸው ደግሞ ቫይረሱ በላቮራቶሪ ውስጥ የተፈጠረ ነው ይላሉ። አንዳንዶቹ ቫይረሱ እዚያው ሁዋን ከተማ የሚገኘ የጄን ላቦራቶሪ ውስጥ የተፈጠረ ነው ሲሉ፣ ቻይናዎች ደግሞ አሜሪካኖች እንደፈጠሩትና ለውድድር የመጡ የአሜሪካን ወታደሮች የእንስሳ ገበያ ላይ ሲዘዋወሩ ከእነሱ ወደ አንደኛው እንስሳ እንደተላለፈ ይናገራሉ። የቫይረሱን ምንጭ አስመልክቶ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቫይረሱ ከአሜሪካን እንደመጣ በግልጽ ተናግሯል። በዚህ አባባል የተበሳጨው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ዋሽንግተን የሚገኘውን የቻይና አምባሳደር በመጥራት ለስቴት ዴፖርትሜንቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተደርጓል። ይህን ዐይነቱን አባባል የኮንስፒረሲ ቲዎሪ አድርገን ብናልፈው በሳይንስ እንደተረጋገጠው የቫይረሶች ምንጮች እንስሳዎች ሲሆኑ፣ ከአንዳንድ እንስሳዎች የሚመነጩት ቫይረሶች ወደ ሰው ከተላለፉ እስከመሞት የሚያደርሱና ከአንደኛው ወደሌላኛው በመራባት ብዙ ሰዎችን እንደሚያጠቁ ነው። ከእነዚህ እንስሳት ውስጥ እንደ ዐይጥ፣ አሳማ፣ ውሻና በአሁኑ ወቅት ደግሞ እንደሌሊት ወፍ የመሳሰሉት የሚበሩና የሚሽለኮለኩ እንስሳዎች ዋና የቫይረስ ምንጮች ናቸው። በአሁኑ በግሎቫላይዜሽን ዘመን በሰዎችና በተለያዩ ዱር አራዊቶች መሀከል ከፍተኛ ቅርርቦሽ ስላለና አንዳንዶችም ለምግብነት ስለሚውሉ እንደኮረና ቫይረስ የመሳሰሉት መከሰታቸውና መተላለፋቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። በዚህ መልክ በታሪክ ውስጥ በተለያየ ወቅት ይህንን የመሳሰሉ የቫይረስ ዐይነቶች በመነሳትና ሰዎችን በመያዝ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አገር በመሸጋገር ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መሞት ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል። እስካሁን ድረስ በአደገኛነቱ የሚታወቀው ስፔይን አገር እ.አ.አ በ1918 ዓ.ም የተከሰተው የስፓንሽ ኢንፍሉዬንዛ የሚባለው ሲሆን፣ የታሪክ ተመራማሪዎች ለ60 ሚሊዮንና ከዚያም በላይ ለሆነ ህዝብ መሞት ዋና ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ይኸው የወረርሽኝ በሽታ በአገራችን ምድር የህዳር በሽታ በመባል ይታወቃል።

ያም ተባለ ይህ፣ እንደዚህ ዐይነት ቫይረሶች በየጊዜው መልካቸውን እየቀያየሩ እንደሚከሰቱና የሰውንም ልጅ የሚፈታተኑ መሆናቸው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ምናልባትም ከ90%(with great probability) ሊሆን በሚችል ሁኔታ የኮረና ቫይረስ ምንጭ ቻይና መሆኗ ይጠረጠራል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ቫይረስ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቻይና አልፎ ወደ ደቡብ ኮርያና ጣሊያን፣ ስፔይንና እንግሊዝ፣ ከዚያም አልፎ አውስትሪያና ጀርመን፣ እንዲያም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ በመዛመት የሰውን ልጅ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መጣሉ የሚያሳዝንም የሚያስገርምም ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቫይረሱ ዋና ማዕከል(Epicentre) ታላቋ አሜሪካ፣ በተለይም ኒዎርክ ከተማ ነው። ይህ ጉዳይ የሚያረጋግጠው የሰው ልጅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን በመስራት እርስ በእርሱ የሚጨፋጨፍ ቢሆንም፣ እንደዚህ ዐይነቱን የረቀቀና በዐይን ሊታይ የማይችል ነገር ሊያሽንፍ እንደማይችል ነው። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ግን ለምንድነው አደጉ የሚባሉ አገሮችን በቀላሉ ማጥቃት የቻለውና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሞቱ የቻሉት? የሚለው ነው። ይህንን ጉዳይ ለመረዳት በአንድ አገርም ሆነ በተለያዩ አገሮች እንደ ፈሊጥ ተደርጎ የሚወሰድና ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ጠጋ ብሉ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። በተለይም የሰውን ልጅ ማዕከል ያላደረገና ከትርፍ ወይንም ከንጹህ ኢኮኖሚ ስሌት ብቻ ተግባራዊ የሚሆንና ጥቂት የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም ፖሊሲ የመጨረሻ መጨረሻ የብዙ ሰዎችን ህይወት መቅሰፉ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና ባህላዊና የስነ-ልቦና ተፅዕኖም ይኖረዋል።

የቁጠባ ፖሊሲና ጠንቁ እንዲሁም የስርዓት ጥያቄ!

እንደምንከታተለው ቫይረሱ የተከሰተባት ቻይና በተለይም ደግሞ የሁዋን ከተማ የቫይረሱ ዋና ማዕከል ቦታ መሆኗ ቀርቶ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔይን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ታላቁ አሜሪካ መሆናቸው የዓለምን ህዝብ እያነጋገረ ነው። አብዛኛዎችም የሚጠይቁት ጥያቄ ቫይረሱ የተከሰተባት ቻይና በምን ተዓምር ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን በመቆጣጠር ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው ሁኔታዋ ለመመለስ መንገድ ላይ መሆን የቻለችው? በማለት ነው። በተለይም ትችታዊ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የስርዓትን ጥያቄ በማንሳት ምናልባት ቻይና የተሻለ አደረጃጀትና ህዝቦቿም ትዕዛዝን የሚከተሉ በመሆናቸው ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የቻለችው በማለት በድፍረት ይናገራሉ። ከዚህ በመነሳት አንዳንዶች ልቅ የሆነ የሊበራሊዝም ስርዓት በተለይም ይህን የመሰለ የወረርሽ በሽታ ሲከሰት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል ይላሉ። ይህን የሚሉበት ምክንያትም የተለያዩ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ከመንግስት የመጣ ትዕዛዝን በጭፍን እንደማይቀበሉና ከመቀበላቸው በፊት ጥያቄ ስለሚያቀርቡና ለእንደዚህ ዐይነት ወረርሽኝ ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለው የሚገምቱትን አስተያየት ስለሚሰነዝሩና ችግሩንም በሌላ መልክ መፍታትም ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ ነው። በሌላ ወገን ግን የተለያዩ አገሮች የተለያየ ልምድና ታሪክ እንዲሁም የአሰራር ስልት ስላላቸው ይኸኛው ብቻ ነው ትክክል ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። ከላይ ለየት ያለ አስተያየት ያላቸው ደግሞ እንዳለ ስርዓቱን ጥያቄ ውስጥ በማስቀመጥ ምናልባትም ካፒታሊዝም በዚህ መልክ መቀጠል እንደማይችል ይናገራሉ። ይሁንና ግን የሚዘነጉት ነገር ቻይና የምዕራቡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን እንደበቃችና ጥብቅ የሆነ መንግስታዊ አገዛዝን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር በማጣመር እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ መድረሷን ነው።

በአለፉት ሰላሳ ዐመታት ቻይና በቴክኖሎጂ መጥቃ በመሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን ህዝቦቿን አደራጅታ አንድ ቢሊዮን አራት መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከድህነት በማላቀቅ ለመከበር በቅታለች። ቀስ በቀስም ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን በመረዳት በሁሉም አቅጣጫ የቴክኖሎጂ ብቃትነትን በማሳየት እንደምናየው ይህንን የመሰለውን አደገኛ ቫይረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር ችላለች። ቻይና እንደዚህ የመሰለው የቴክኖሎጂ ብቃትነት ላይ የደረሰችው በዲሲፒሊን የተደራጀና ሚናውን የሚያውቅ የፖለቲካ አመራር ስላላት ነው። በሁሉም መስክ የምዕራቡን ዓለም መቅደም አለብኝ የሚልና በትጋትና በተዕግስት፣ እንዲሁም በቆራጥነት የሚሰራ የፖለቲካ ኤሊት ስልጣኑን በመያዙ ነው። „ዕውቀት ኃይል ነው“ የሚለውን የሳይንቲስቱን የፈራንሲስ ባኮንን አባባል በጭንቅላቱ ውስጥ በመቅረጹና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛ ወጪ ስለሚመድብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቻይና እንደዚህ ዐይነቱን ድል ለመቀዳጀት በቅታለች። የፖለቲካ ኤሊቱ ጭንቅላቱ በአሻጥርና በትናንሽ ነገሮች ያልተያዘ በመሆኑ ሁሉም በአንድ መንፈስና ለአንድ ዓላማ በከፍተኛ ዲሲፒሊን የሚሰራ ነው። የአገሬንና የህዝቤን ዕድል ሌላ የውጭ ኃይል ሳይሆን እኛ ራሳችን ብቻ ነን መወሰን ያለብን በማለት በፖለቲካ ኤሊቱና በአብዛኛው ምሁር ዘንድ ስምምነትና ተባብሮ የመስራት ፍላጎት አለ። ስለሆነም ብዙ የምርምርና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቂያና ማዳበሪያ ማዕከሎችን በየቦታው በመዘርጋትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስና በመደጎም እንደምናየው የብዙ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምዕራቡን ዓለም በተለይም አሜሪካንን እየተፈታተነው ይገኛል። ካለቴክኖሎጂና በየቦታው ካልተዘረጋ የምርምር ማዕከል አንድን ህዝብ መመገብም ሆነ ከእንደዚህ ዐይነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊበክል የሚችል ቫይረስም ሆነ ሌላ በሽታ ለመዋጋት እንደማይቻል ቻይና ለማረጋገጥ ችላለች። እንደሰማነውና እንደተከታተልነው የቫይረሱን መራባት ከሞላ ጎደል መቆጣጠር ከቻለች በኋላ ጣሊያንን ለመርዳት ሀኪሞችና የህክምና መሳሪያዎችን ልካለች። በዚህ ዐይነቱ ትብብር ኪዩቫና ራሺያም በመታከል ብዙ ሀኪሞችና የህክምና መሳሪያዎችን ወደ ጣሊያን ልከዋል። ራሺያ በበኩላ ደግሞ እንደዚሁ አሜሪካንን ለመርዳት የህክምና መሳሪያዎችን ልካለች። የተገለበጠ ዓለም!!

ለምንድን ነው ጣሊያንም ሆነ ስፔይን፣ እንዲሁም እንግሊዝ፣ አሁን ደግሞ አሜሪካ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኮቪድ 19 በቀላሉ ሊጠቁና የብዙ ሰዎችም ህይወት ሊቀጠፍ የቻለው? እንደሚታወቀው፣ በተለይም በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ግንዛቤን ያላገኘው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ እስከ 1970 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በብዙ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት ለሰፊው ህዝብ ግልጋሎት የሚሰጡና ሰራተኛው በሚከፍለው ቀረጥ የተሰሩ ሃኪም ቤቶችንና ሌሎች እንደ ውሃና መብራት እንዲሁም ጋዝ የመሳሰሉትን በመቆጣጠር በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቦቻቸው ያቀርቡ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ የመዋዕለ-ነዋይ ፍሳሽ በማደረግ የህዝቦቻቸው አለኝታ በመሆን በተለይም በህክምናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ርብርቦሽ በማድረግ ብቃትነትን ያሳዩ ነበር። በእነዚህ የህዝብ መገልገያዎች ላይ መንግስት የሚያደርገው ጣልቃ-ገብነት ያልጣማቸው ኃይሎች መንግስት እጁን እንዲያነሳና ሁሉኑም ነገር ለገበያው ተዋንያን መልቀቅ አለበት በማለት ከፍተኛ ግፊት ያደርጋሉ። ወቅቱ ግሎባላይዜሽንየጀመረበት ዘመን ስለነበርና ሁሉም በዚህ ዙሪያ ስለሚከንፍ መንግስታት ከየአቅጣጫው የሚመጣባቸውን ግፊት መቋቋም አልቻሉም። በተለይም የኃይል ሚዛኑ በግሎባላይዜሽን ዙሪያ ለተሰበሰቡ ኃይሎች ያደላና የርዕዮተ-ዓለም ሽግሽግም ስለነበር ከፍተኛ ግፊት ያደርጉ የነበሩት ትላልቅ የአሜሪካ አማካሪ ኩባንያዎች፣ እንደ መኪንሲይና(McKinsey) ከጀርመን ደግሞ እንደ ሮላንድ በርገር የመሳሰሉት አማካሪ ኩባንያዎች(Consulting Companies) ናቸው። መንግስታት ሳይወዱ በግድ በጥገና ፖሊሲ አማካይነት ሆስፒታሎችንና ሌሎች የህዝብ መገልገያ ዘርፎችን ኢንቬስተሮች ለሚባሉት በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ ይገደዳሉ። በአማካሪ ድርጅቶች ፍልስፍና ሁሉም ነገር ከትርፍ አንፃር መስራት አለበት። የአንድ ግልጋሎት የሚሰጥም ሆነ ሌላ ድርጅት ብቃትነቱ ሊለካ የሚችለው ትርፋማ ሲሆን ብቻ ነው። መሰረታዊውና ቅድሚያ የሚሰጠው ጥያቄ የሰውን ልጅ ፍላጎት ማሟላት ሳይሆን በመጀመሪያ ደረጀ ማንኛውም ገንዘብ የሚወጣበት መንግስታዊም ሆነ የግለሰብ ድርጅት ከትርፍ አንፃር መሰላት አለባቸው። ስለሆነም መንግስታት ወጪ ለመቆጠብና ትርፍም ለማግኘት ሲሉ በህዝብ ቀረጥ የተሰሩ ሃኪምቤቶችንም ሆነ ሌላ ድርጅቶችን ይሸጣሉ፤ ወይም ደግሞ በከፊል በገንዘብ የናጠጡ ኩባንያዎች ድርሻ(Share) እንዲገዙ ያደርጋሉ። የሀብታሞችንና የትላልቅ ኩባንያዎችን ገንዘብ የሚያስተዳድሩት እንደ ብላክ ሮክ የመሳሰሉ የአሜሪካን ሄጅ ፈንዶች በመዋዕለ-ነዋይ ስም ድርሻ በመግዛት የትርፉ ተቋዳሽ ይሆናሉ። የግል ኢንቬስተር ደግሞ አንድን ድርጅት ሲገዛ ወይም ድርሻ በመግዛት በመዋዕለ-ነዋይ መልክ ሲሳተፍ ዋና ዓላማው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከልና የስራ-መስክ በመክፈት በአንድ አካባቢ ያለን ህዝብ ለመጥቀም ሳይሆን በትንሽ ወጪ እንዴት አድርጌ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት እችላለሁ ከሚለው ስሌት በመነሳት ነው። ለዚህ ዐይነቱ የሀብት ሽግሽግ ዋናው ተዋናይ ደግሞ በ1979ና በሰማኒያኛው ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝ ሚስስ ቴቸር ሲሆኑ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ አዲሱ ሌበር በሚል ስሙን እንዲቀይር ያደረጉት የሌበር ፓርቲ ሊቀመንበርና ስልጣንን የተረከቡት ቶኒ ብሌየር ናቸው። ቶኒ ብሌየር እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስተርነት በሚያሰትዳድሩበት ወቅት የወይዘሮ ቴቸርን የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ ልዩ መልክና ፍጥነት በመስጠት ገበያውን ለውጭ የመዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾች ልቅ በማድረግ ህዝባቸውን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ ናቸው። ከተለያዩ አገሮች፣ ከሳውዲ አረብያ፣ ከካታር፣ ከራሺያና ከቻይና ከመሳሰሉ አገሮች በገንዘብ የናጠጡ ከበርቴዎች በመምጣትና በተለይም ትላልቅ አፓርትሜንቶችን በመግዛት እራሱን የለንደንን ኗሪ ህዝብ ከተማውን ጥሎ እንዲወጣ ያደረጉ ናቸው። በህክምናው መስክም እንደምንሰማውና እንደምናየው ከፍተኛ ድክመት ይታያል። በቁጠባ ፖሊሲ የተነሳ አብዛኛዎቹ ሃኪም ቤቶች አስፈላጊውን መሻሻል ያላገኙና ለእንደዚህ ዐይነት ወረርሽኝ ያልተዘጋጁ ናቸው። እኝህ ሰው ስልጣናቸውን ለጎርደን ብራውን ካስረከቡ በኋላ የአንድ የአሜሪካን እንቬስትሜንት ኩባንያ ተቀጣሪ በመሆን በዐመት ሶስት ሚሊዮን ዶላር ይከፈላቸዋል። ስራቸውም የአፍሪካ መንግስታትን „ማማከርና“ የጥሬ-ሀብቶቻቸውን ለትላልቅ የአሜሪካና የእንግሊዝ ኩባንያዎች እንዲሸጡ ማድረግ ነው። በተጨማሪም በአማካሪነት ስም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት መፍጠርና በተለያየ መልክ ሀብት ከአፍሪካ ምድር ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚተላለፍበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው። ለዚህ ዐይነቱ ፀረ-ዕድገት ተግባር የአፍሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ኤሊት ይተባበራቸዋል። እስከዚህም ድረስ የተወሳሰበ ዕውቀት የሌላቸውና አርቀውም የማያስቡ የአፍሪካ መሪዎች የእነ ቶኒ ብሌየርን ዐይነት የመሳሰሉ ሰዎችን ምክር በመስማት አገሮቻቸውን ከፍተኛ መቀመቅ ውስጥ ከተዋቸዋል፤አሁንም እየከተቱ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚጠቅም ኢኮኖሚያዊ ስርዓት መገንባት አልተቻለም።

ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሌበራል አስተሳሰብ እንደ አዲስ ፈሊጥ በመታየቱና ተግባራዊም በመሆኑ እንደ ጣሊያንና ስፔይን የመሳሰሉትንም አገሮች ከውስጥ ሊያዳክማቸው ችሏል። ስትራቴጂክ በሆኑ ነገሮች ላይና ከረጅም ጊዜ አንፃር ከማሰብ ይልቅ ይህንን ዐይነቱን ፖሊሲ በመከተላቸው ዛሬ እንደምናየው በተለይም በዕድሜያቸው የገፉና በቀላሉ ሊድን የማይችል በሽታ የያዛቸውን ሰዎች ኮረና ቫይረሱ በቀላሉ ሊያጠቃቸው ችሏል። በተለይም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም በሚሰጡ እንደ ጤና ድርጅቶች በመሳሰሉት ላይ ከመረባረብ ይልቅ ሃኪም ቤቶችን መሸጥና ሰራተኞችን ማባረር ዋናው የመንግስቱ ፖሊሲ ሆነ። በተለይም በቫይረሱ የተጠቃው የደቡቡ የጣሊያን ክፍል ሳይሆን በኢንዱስትሪ የበለጸገው ሎምባርዳይ የሚባለው ግዛት ነው። የዜና ማሳራጫዎች እንደሚያወሩት ከሆነ ከፍተኛ የአየር መበላሸት ያለበትና በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች የሚኖሩበት ግዛት ነው። አሁን ቀስ በቀስ እያሉ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በኮረና ቫይረስ በቀላሉ የተጠቁት ሰዎች ሌሎች ቫይረሶችን ለመከላከል ይችላሉ ተብለው የታመኑ የክትባት መድሃኒቶችን የተወጉ ናቸው። በተጨማሪም ሁሉንም ባክቴሪያኖች ሊያጠቃ ይችላል ተብሎ የሚገመት አንቲ-ባዮቲኩም(Broad Spektrum) ክኒን የዋጡ ሰዎች በኮረና ቫይረስ በቀላሉ ሊጠቁ ችለዋል። ምክንያቱም በየጊዜው አንቲ-ባዮቲኩምን መውሰድ የሰውነትን ከበሽታ የመከላከል ኃይል ስለሚቀንስ ነው። በጣሊያንም ሆነ በተቀሩት የአውሮፓ አገሮች በየክረምቱ ኢንፍሎዬንዛን የመሳሰሉ የወረርሽኝ በሽታዎች ለመከላከል በሚል ቀደም ብለው የሰውነትን በሽታን መከላከል የሚያዳክሙ አጠቃላይ የሆነ አንቲ-ባዮቲኩም ክኒኖችን ይውጣሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአብዛኛው ህዝብ በሽታን የመከላከል አቅም የደከመ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በቁጠባ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎች ሃኪሞች ቤቶች በህክምና መሳሪያና መድሃኒት እንዲሁም በሀኪሞች ዕጥረት እንዲዳከሙ ሆነዋል። ከዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ወይም ሁሉንም ነገር የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ይፈታዋል ከሚለው ባሻገር በአለፉት አርባ ዐመታት ጣሊያን ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚታይባትና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የሰራተኛውንም ሆነ የጠቅላላውን ህዝብ መብት ያስጠብቁ የነበሩ እንደ ኮሙኒስትና የክርስቲያን ፓርቲ የመሳሰሉት ባህላዊና አገር-አቀፍ ፓርቲዎች እንዳሉ ወድመዋል፣ ወይም ደግሞ ትርጉም እንዳይኖራቸው ለመደረግ በቅተዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የፖለቲካው ሜዳ ክፍት በመሆኑ ለህዝብ ግልጋሎት መስጠት የሚችሉና የሚገባቸውም እንደ ሃኪምቤቶች የመሳሰሉት ሊዳከሙ ችለዋል። ስለሆነም በቫይረሱ የተደናገጠው ወደ ሃኪምቤት ሲጎርፍ ሃኪም ቤቶች እየተንጋጋ የሚመጣውን ህዝብ ማስተናገድ አልቻሉም። በአንፃሩ ግን ጥቂቶች የዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ ተጠቃሚ በመሆን አትራፊ ሆነዋል።

የስፔይንም ሁኔታ ከዚህ ያነሰ አይደለም። ከፍራንኮ መሞት በኋላ አዲስ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ቢፈጠርም በፓርቲዎች ዘንድ ሙስና የተስፋፋ ነው። እንደጀርመን ሰፋ ያለ ትችታዊ አመለካከት የዳበረበት ምሁራዊ ኃይል ያለበት አገር አይደለም። ከታሪክ አንፃርም የሃይማኖት መሪዎችና የመሬት ከበርቴዎችም ሆነ የአሪስቶክራሲው መደብ እንደሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከበርቴያዊ ወይም ሊበራል አስተሳሰብ እንዳይመጣ አጥብቀው ይታገሉ ነበር። ስለሆነም በስፔይን በፍራንኮ ዘመንም ሆነ በኋላ የተገለጸለት የሲቭል ማህበረሰብ ብቅ ሊልና የፖለቲካ ኃይል ሊሆን አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰከነና በተለይም የሰፊውን ህዝብ ኢኮኖሚ ኃይል የሚያዳክሙ እንደ ኒዎ-ሊበራል የመሳሰሉ ኢኮኖሚ ፖሊስዎችን የሚዋጋ የተጠናከረ ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ኮንሰርቫቲብ ነን የሚሉና የክርስቲያንን ስም የለጠፉ ፓርቲዎች ፣ በመሰረቱ የክርስቲያን ሞራልም ሆነ እሴት የሌላቸው ንጹህ በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ የመጨፈሪያ ሜዳ ማግኘት ችለዋል። በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በኮንሰርቫቲምና በክርስቲያን ስም የተደራጁ ፓርቲዎች በመሰረቱ የሚያካሂዱት ፖለቲካ ወደ ኋላ የቀረና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅምና በተለያዩ ፖሊሲዎች አማካይንት ሀብታሙን የባሰ ሀብታም የሚያደርጉ ናቸውው። በተለይም በማድሪድና አካባቢዋ ስልጣንን የያዘው የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ የህ ወደ ሰላሳ ሚሊያርድ ዶላር የሚያህል ገንዘብ „ሲቆጥብ“ ፣ በዚያው መጠንም ወደ ሰላሳ ሺህ የሚጠጉ የሃኪም ቤት ሰራተኞችን አባሯል። ይኸው እንደምናየው እንደዚህ ዐይነት አደገኛ ወረርሽኝ ሲከሰትና ብዙ ሰዎችን ሲያዳርስ እየተንጋጋ የሚመጣውን ህዝብ ሃኪም ቤቶች ለማስተናገድና ለማከም በቂ አልጋና ነርሶች የላቸውም። በዚህም ምክንያት ቫይረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊራባ የቻለው በተለይም በሃኪም ቤቶችና ሽማግሌ ሰዎችን ማኖሪያ ቦታዎች አካባቢ ነው። በተለይም በፍርሃት ተውጠው ወደ ሃኪም ቤት የመጡት በቀላሉ በቫይረሱ ሊጠቁ ችለዋል። በዚህ መልክ ሁሉም ነገር ከትርፍ አንፃር ብቻ እንዲታይ በመደረጉ በየሃኪም ቤቶችም አዳዲስ ሃኪሞችንና ነርሶችን ከመቅጠር ይልቅ ያሉትንም በመቀነስ በተቀሩት ሰራተኞች ላይ የስራ ጭነት ሊደራረብ ችሏል።ይህ ብቻ ሳይሆን ከ1990ዎቹ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ግሎቫላይዜሽን የሚባለው ፈሊጥ በተስፋፋበት ዘመን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይፈስ የነበረው በቴክኖሎጂ መስክ ላይ ሳይሆን የአየር ባየር ቁማር ላይ ወይንም ቤቶችን በመስራትና በመሸጥ ላይ ስለነበር ህዝባዊ ግልጋሎት የሚሰጡ የህክምና ድርጅቶች የመሳሰሉት ተዘንግተው ነበር ወይንም ደግሞ አትኩሮ አልተሰጣቸውም ነበር ማለት ይቻላል።

ወደ አሜሪካ ስንመጣም ሁኔታው ከዚህ የባሰ ነው። አሜሪካ ሙሉ በሙሉ „ግለሰብአዊ ነፃነት“ ተግባራዊ የሆነበት አገር ነው ተብሎ ስለሚሰበክ ይህ የተዛነፈ አስተሳሰብ በሰፊው ህዝብ አዕምሮ ውስጥ እንዲቀረፅ ተደርጓል። በተለይም የገበያ ፖሊሲ አክራሪነትን የሚያራምደው የኮንሰርቫቲብ ምልክትና የክርስትናን ሀይማኖት የለጠፈው የሪፓብሊካን ፓርቲ ፎክስ ሚዲያን በመጠቀም የሰፊውን የአሜሪካን ህዝብ ጭንቅላት ሊሰልበው ችሏል። የስለሆነም መንግስት ጣልቃ የሚገባበት ነገር በሙሉ እንደ እርኩስ ስራ የሚታይና ነፃነትንም ሙሉ በሙሉ ይጋፋል ተብሎ ስለሚታመን በተለይም ተከታታይ ገቢ የሌለው ወይም ደሞዙ ዝቅተኛ የሆነ ሰው ለጤንነት መድህንም ሆነ ታሞ ሃኪም ቤት ሲሄድ ለህክምና መክፈል አይችልም። በአሁኑ ጊዜ የጤንነት መድህን የሌለው ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካን ህዝብ እንዳለ ይታወቃል። በሌላ ወገን ግን የአሜሪካ መንግስት ለመከላከያና ለጦር መሳሪያ መግዢያ በየዓመቱ እስከ $800 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ያወጣል። ሰልሆነም በአሜሪካን ምድር ልክ እንደ አውሮፓው፣ በተለይም እንደ ጀርመን አገር እኩል በሆነ ደረጃ አሰሪዎችንም ለጤንነት መድህን (Health Insurance) ወጪ የሚያሳትፍ ባህልና ህግ የለም። በጀርመን አገር ሰራተኛውም ሆነ አሰሪዎች በተለይም እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በእኩል ደረጃ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ህግ ነበር። እስከ 1990 ዓ.ም መግቢያ ድረስ ደግሞ መድሃኒቶች በሙሉ ከመድህን ክፍያው ጋር የተጠቃለሉ ስለነበሩ ማንኛውም ታማሚ ለመድሃኒት በተጨማሪ አይከፍልም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን የጥገና ለውጥ አደረግን በማለት እንደሰው ገቢ መጠን አንድ ሰው ለመድሃኒት አምስት ኦይሮ ይከፍላል። ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ አብዛኛውን ህዝብ የጎዳውና ያስመረረው አይደለም። በተጨማሪም በጀርመን ምድር አንድ ሰው የጤንነት መድህን ይኑረው አይኑረው ከታመመ ዝም ብሎ ሜዳ ላይ አይወድቅም። በተለይም ከቤተክርስቲያን ጋር የተቆላለፉ የህክምና መስጫ ጣቢያዎች ስላሉ እዚያ ሄዶ መታከም ይችላል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአሜሪካን ምድር ያለው ልምድ እጅግ ወደ ኋላ የቀረና አደገኛና አሳሳች አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን የተረዱት ባራክ ኦባማ „ኦባማ ኬር“ በሚል ተግባራዊ ለማድረግ ከሪፓብሊካኖች ዘንድ ብዙ ተቃውሞ እንደተነሳባቸውና ከብዙ ክርክርና ማሳመን በኋላ ተግባራዊ ለመሆን እንደበቃ እንገነዘባለን። ይሁንና የኦባማ ኬር የተወሳሰበና አድካሚ በመሆኑ ሁሉንም የጠቀመ አልነበረም። ፕሬዚደንት ትረምፕ ስልጣንን ከተቆጣጠሩ በኋላ በዚህም በዚያም ብለው የኦባማ ኬር እንዲሸራረፍ ለማድረግ በቅተዋል። ይኸው እንደምናየው የዚህ ዐይነቱ ሁሉንም ነገር ገበያው ይፈታዋል የሚለው አካሄድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ቫይረሱም በፍጥነት በመራባት ከኒዎርክ አልፎ ኒው ኦርሊየንስና ኮሎራዶ በመዳረስ ቀስ በቀስም ሁሉንም የአሜሪካ ግዛቶች እያዳረስ ነው።

እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ሁሉንም ነገር ገበያው ይፈታዋል ከሚለው ባሻገር ለምን እንደ አሜሪካን የመሳሰለው አገር የሚኖረው ህዝብ በቀላሉ የቫይረሱ ተጠቂ ለመሆን እንደበቃ ጠጋ ብሎ መመልከቱ ለእኛም ይጠቅማል ብዬ እገምታለሁ። በአሜሪካንም ሆነ በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች አብዛኛዎች ምግቦች በፋብሪካ ውስጥ የተፈበረኩና ልዩ ልዩ ኬሚካሎች እየገቡባቸው የሚመረቱ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የምግብ ዐይነቶች ለሰውነትና ለአዕምሮ ገንቢ የሆኑ ንጥረ ነገሮችንና እንደፕሮይቲንና ሌሎችም የሰውነት ገንቢ ሚኒራሎች በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙባቸው ናቸው። ከዚህም በላይ አብዛኛዎቹ ምግቦች ጨው፣ ቅባትና ስኳር የበዛባቸው ከመሆናቸው የተነሳ ምግቡን ሆድ ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርጉ እንጂ ይህን ያህልም ለጤንነት አዎንታዊ አስተዋፅዖ አያደርጉም። ውጭ በየመቆሚያ ቦታዎች የሚሸጡት አንደ ማክንዶናልድና ፖምፕፍሪትስ የመሳሰሉት ምግቦችም ደግሞ ሆድን ከመሙላትና ጤንነትን ከማቃወስ በስተቀር ለሰውነትም ሆነ ለአዕምሮ መጎልመስ የሚሰጡት ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከዚህም በላይ እንደኮካላና ስፕራይት የመሳሰሉት በተለይም በወጣቱ ዘንድ በብዛት የሚጠጡት ጣፋጭ መጠጦች ገንቢ ሳይሆኑ ጤንነትን የሚያቃውሱ ናቸው። እንደሚታወቀው የተሟላና ተፈጥሮአዊ የሆነ የምግብ ዐይነት ከበቂ እንቅልፍና ስፖርት ጋር በመዳበል የሰውነትን ከበሽታ የመከላከል ኃይል ያጎለምሳል። ሴሎቻችን ገንቢ የሆኑ ምግቦችን ሲያገኙ በሽታን የመከላከል ኃይል ያገኛሉ። ይህ ጉዳይ በምግብ ሳይንስ አዋቂዎችና በተገለጸላቸው ሃኪሞች ተደጋግሞ የሚወሳና በሲቪል ማህበረሰብም የሚሰበክ ጉዳይ ነው። ይህ ዐይነቱ በብዛትና ከትርፍ አንፃር ብቻ የሚመረት የምግብ ዐይነት በተለይም በአሜሪካን አገር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የጥቁር አሜሪካኖችንና የተቀረውን የህብረተሰብ ክፍል ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ እያቃወሰ ይገኛል። የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊትና የኩላሊት መበላሸትና ሌሎች የስልጣኔ በሽታዎች ተብለው የሚጠሩት በሙሉ የዚህ ዐይነቱ በኢንዱስትሪ ደረጃ እየተዘጋጀ ከሚቀርብ የምግብ ዐይነት ጋር የተያያዙና በተለይም ጥቁር አሜሪካኖችንና ላቲን አሜሪካኖችን የሚያጠቁ ናቸው። ስለሆነም አስፈላጊውን የተመጣጠነ የምግብ ዐይነት መመገብ የማይችሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና በዕድሜያቸው የገፉ፣ በተለይም ከሰማንያ ዐመት በላይ የሆናቸው በኮረና ቫይረስ የመጠቃት ኃይላቸው ከፍተኛ ነው። ስታትስቲክሱም ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የገበያ ኢኮኖሚ ልቅነትና የትላልቅ ኢንዱትሪዎች የበላይነትን መቀዳጀት በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች የሰውነትና የአዕምሮ ቀውስ እያስከተለ ነው። ከዳየት መቀየር ጋር በተያያዘ የሰዎች የማሰብ ኃይልና ነገሮችን ማገናዘብ በጣም እየደከመ መጥቷል ማለት ይቻላል። በተለይም በአሜሪካን አገር አመጽ መስፋፋቱና ሰውን መግደል ከእንደዚህ ዐይነቱ ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ፣ የአመጋገብ ሁኔታና ማህበራዊ ግኑኝነት መበጣጠስ ጋር የተያያዘ ነው። ሰሞኑን እንደምናየው ሰዉ ምግብ ለመግዛት ከመሰለፍ ይልቅ ሽጉጥ ለመግዛት ሲሰለፍ ይታያል። በተጨማሪም የአመጽ መስፋፋት የአገዛዙ ወይም የሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ አወቃቀር ነፀብራቅ ነው። በሌላ አነጋገር የመንግስቱ መኪና የጠቅላላውን የአሜሪካ ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀ ሳይሆን ከሚሊታሪውና ከስለላ ድርጅቱ ጋር የተሳሰረውን የጥቂት ኦሊጋርኪውን መደብ ነው። ይህ ዐይነቱ መንግስታዊ አደረጃጀት የግዴታ ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል በመዛመትና እንደ ጤናማ አስተሳሰብ በመወሰድ አመጽ የጠቅላላው ህብረተሰብ ፈሊጥ ይሆናል።

ወደ ጀርመን ስንመጣ ደግሞ ሃኪም ቤቶችን ወደ ግልሀብትነት እንዲዘዋወሩና ቁጥራቸው ከሶስት መቶ በላይ የሚበልጡ ሃኪም ቤቶች እንዲዘጉ የተደረጉት በጊዜው ቻንስለር በነበሩት በሚስተር ጌርሃርድ ሽሩደር አማካይነት ነው። በጊዜው ስልጣንን የተቀዳጁት የሶሻል ዲሞክራቲክና የአረንጓዴው ፓርቲ የጥምር መንግስት በብላክ ሮክና ሮላንድ በርገር በሚባለው በጀርመን አማካሪ ድርጅት በመመከር የሰራተኛውን መብት የሚቀንስ አጀንዳ 2010 ተብሎ የሚጠራ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታ ለአሜሪካን ትላልቅ የገንዘብ አስተዳዳሪዎች በሩን ያመቻችላቸዋል። ብዙ ሃኪም ቤቶችም ወደ ግል ሀብትነት ይለወጣሉ። በተለይም ሃኪም ቤቶች የግዴታ ከትርፍ አንፃር መስራት አለባቸው በማለት ሃኪሞች ከህክምና ተግባራቸው በተጨማሪ በአስተዳደር ስራ እንዲጠመዱ ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአብዛኛው የጀርመን ሃኪም ቤቶች ሃኪሞችና ነርሶች ከሚፈለገው ሰዓት በላይ ይሰራሉ። ይህንን ዐይነቱን የስራ ጭነት ለመሸከም የማይፈልጉ የተሻለ ገንዘብ ወደ ሚከፈልበትና የስራ ጭነት በሌለበት እንደ ስካንዲኔቪያንና እንደ ስዊዘርላንድ የመሳሰሉት አገሮች ይሄዳሉ። በኮረና ቫይረስ መራባት የተነሳ የተደናገጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስተሩና በጤናው መስክና ኃላፊነት ያላቸው የሰራተኛ ሚኒስተር ይህንን ጉዳይ በማንሳት ወደፊት ሃኪም ቤቶች ከትርፍ አንፃር ሳይሆን ለተማሚው ህዝብ አስፈላጊውን የህክምና ዕርዳታ መስጠት እንዳለባቸውና ወደፊት በዚህ መንፈስ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በተጨማሪም በህክምና መሳሪያዎችና የአፍና የአፍንጫ መከላከያዎች በቻይና መመካት እንደሌለባቸውና በማንኛውም የህክምና መሳሪያ ላይ ራሳቸው ማምረት እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ ደርሰዋል። ለዚህም ብዙ ገንዘብ መድበዋል። ይሁንና በጀርመን ምድር የተወሰኑ ሃኪም ቤቶችን ወደግል ቢዘዋወሩና ከትርፍ አንፃርም ቢሰሩ በውስጥና በሰራተኛው ማህበር በተደራጁ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞና ስላለና ክርክርም ስለሚደረግ እንደ ስፔይንና ጣሊያን እንዲሁም አሜሪካ የሃኪም ቤቶች ሁኔታ የተበላሽና የሚያስመርር አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ እንደተፈራው ሳይሆን በኮረና ቫይረሱም የተጠቃና በቫይረሱም ምክንያት የተነሳ የሞተ ሰው ቁጥር ይህን ያህልም የተጋነነ አይደለም።

አጠቃላዩን ሁኔታ ስንመለከት ሁሉንም ነገር ገበያው ሊፈታው ይችላል የሚለው አምልኮ በተለይም እንደዚህ ዐይነት ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ በፍጹም ሊሰራ እንደማይችል እያረጋገጠ ነው። የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ሁኔታ የሚያረጋግጠው ይህንን ነው። በገበያ ኢኮኖሚ ስም ተግባራዊ የሆኑ „የጥገና ለውጦች“ በሙሉ ወደ ተሟላና ሰፊውን ህዝብ ወደሚጠቅም ስርዓት አላሸጋገሯቸውም። የሚገርመው ነገር ከዚህ ቀደም በመንግስት ስር ያሉ ሃኪም ቤቶችም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች የግዴታ ወደ ግል መዘዋወር አለባቸው ብለው ይወተውቱ የነበሩ የንጹህ ገበያ ኢኮኖሚ አራማጆች አሁን ተመልሰው የግዴታ መንግስት ጣልቃ መግባት አለበት እያሉ በመወትወት ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ መንግስታት ሁኔታውን ገርበብ ለማድረግ እየተሯሯጡ ነው።

ሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂና አሉታዊ ውጤቱ!

የቫይረሱን መራባት ለመግታት ሲባል የተለያዩ አገሮች የተለያየ ስትራቴጂ ተከትለዋል። ቻይናና ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ስዊድን የተከተሉት፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስፔይንና አሜሪካ ከተከተሉት ለየት ያለ ነው። ቻይናዎች የቫይረሱን በፍጥነት መራባት ከተመለከቱ በኋላ ሁሉንም የመዝጋትና ሰዎችን ቤታቸው እንዲቆዩ በማድረግ የቫይረሱን ምንጭ በመከታተል ቶሎ ብለው ሁኔታውን ለመቆጣጠር ችለዋል። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ቫይረሱ የያዛቸውን ሰዎች ካልያዘቸው በመነጠል ሁሉንም በስማርት ፎን በመከታተልና የደምና የምራቅ ሙከራ በማድረግ የቫይረሱን መስፋፋት መቆጣጠር ችላለች። በተለይም ደግሞ በህክምናው ዘርፍ ላይ ያፈሰሱት ገንዘብና ሀኪም ቤቶችም በብቃትነት እንዲሰሩ ማድረጋቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። ወደ ስዊድን ስንመጣ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሁሉንም ድርጅቶች የመግዛት ስትራቴጂ በመከተል ሳይሆን ለቫይረሱ ጊዜ እንዲሰጠው በማድረግ እያንዳንዱ ሰው የራሱን የመከላከል ኃይል እንዲያዳብር ጥረት አድርገዋል። ይሁንና በየቦታው ከ500 ሰዎች በላይ መሰብሰብ አይፈቀድም። ኪንደር ጋርተኖች በሙሉ ሲከፈቱ፣ ትምህርት ቤቶች ደግሞ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ብቻ ክፍት ናቸው። ሬስቶራንቶችና መጠጥ ቤቶችም ክፍት ናቸው። ይሁንና ግን ሰው ሁሉ በተቻለ መጠን ማህበራዊ ግኑኝነቱን ማላላት እንዳለበት መንግስት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ሰውም ወደ ሌላ አገር ሄዶ መመለስም ሆነ የሌሎች የአውሮፓ አገር ሰዎችም ወደ ስዊድን መግባት ይፈቀድላቸዋል። በተለይም ሰው በዕረፍት ጊዜው በረዶ ቦታዎች ሂዶ የሚሮጥባቸው ቦታዎች ለጎብኝዎች ክፍት ናቸው። አብዛኛውም ሰው ይሰራል። ሆኖም እንደሌሎች የአውሮፓ አገርች ቫይረሱ አልተራባም።

ወደ ጀርመን ስንመለስ ግን ከምግብ መሸጫ መደብሮች በስተቀር ሁሉንም መደብሮች መዝጋት አለብን ወደ ሚለው ስትራቴጂ አድልተዋል። ብዙ ፋብሪካዎች፣ ኪንደር ጋርተኖችና ትምህርትቤቶች እንዳሉ፣ ሬስቶራንቶችና የመጠጥ ቤቶች፣ ማንኛውም ዐይነት የልብስ መሸጫ መደብር ሁሉ ተዘግተዋል። ከሁለት ሰውም በላይ መገናኘት ወይም አብሮ መሄድ አይፈቀድለትም። በተለይም በከፍተኛ የምርት ክንውንና እንደሰንሰለት ለተያያዘውና ይህም እንደባህል በሚቆጠርበት እንደጀርመን በመሰለ አገር ሁሉንም ነገር የመዝጋቱ ስትራቴጂ በተለያዩ ቫይሮሎጂስቶችና በዚህ አካባቢ ጥናት በሚያደርጉ በታወቁ ሀኪሞች ዘንድ በተለያየ መነፅር ነው የሚታየው። በመንግስቱ ስር ያለ ሮበርት ኮኽ የሚባል የምርምር ጣቢያ መሰረትና መንግስትንም በሚያማክረው አመለካከት ስትራቴጂካሊ አስፈላጊ ናቸው ከሚባሉት በስተቀር ሁሉም መዘጋት አለባቸው ስላለ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑ ድርጅቶችና የምግብ ቤቶች በሙሉ ተዘግተዋል። ኳስ መጫወትና መለማመድም ክልክል ነው። ይህን የመሰለውን ሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂ የሚቃወሙና የስዊድንን ስትራቴጂ እንከተል የሚሉም አሉ። በተለይም ሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂ የሚቃወሙት ቁጥራቸው እየበዛና የሚሰጡትም ትንተና አስተማማኝና ግልጽነት ያለበት ነው። አብዛኛዎችም በትላልቅ የዩንቨርሲቲ ሃኪም ቤቶችና በመንግስት በሚደጎመው እንደ ማክስ ፕላንክ የመሳሰሉ የምርምርና የቴክኖሎጂ አፍላቂ ተቋማት የሚሰሩ ፕሮፌሰሮች ናቸው። ይሁንና ግን የጀርመን መንግስት ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከተለያዩ ተቋማትና ፕሮፌሰሮች የሚቀርበውን አማራጭ ሃሳብ የሚያዳምጥ ሳይሆን ሮበርት ኮኽ ከሚባለው በመንግስት በሚደገፈው የቫይሮሎጂና የተለያዩ የትሮፒካል መመርመሪያ ተቋማት የሚመጣውን ሃሳብ ብቻ ነው። ከጤና ጥበቃ ሚኒስተሩም ሆነ ከወይዘሮ መርክል ጋር በመሆን ስለቫይረሱ መግለጫ የሚሰጡትና በግራፍ መልክ የሚያስረዱት ከዚህ ተቋም የሚመጡ ሳይንቲስቶች ብቻ ናቸው። ይህ ዐይነቱ ሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂ በጀርመን ህዝብ ዘንድ ለጊዜው በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘ ቢሆንም በየጊዜው ግን ድጋፍ እያጣ የመጣ ይመስላል።

በዚህ ዐይነቱ ሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂ ብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጠቅተዋል፤ የከሰሩም አሉ። አንዳንዶችም ከእንግዲህ ወዲያም ተመልሰው የማንሰራራት ኃይላቸው በጣም ደካማ ነው። እንደ ሉፍታንሳ የመሳሰሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ከሚባሉት የአየር መንገድ ኩባንያዎች የሚሰለፈው በረራውን 90% ያህል ቀንሷል። እነዚህን የመሳሰሉና፣ ሆቴል ቤቶችም ሆነ የማምረቻ መደብሮች በመዘጋታቸው ኢኮኖሚው ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል። ኢኮኖሚውም እርስ በእርሱ የተሳሰረ ስለሆነ በተለይም የትላልቅ ኩባንያዎች መዘጋት ትናንሾችንም በጣም አዳክሟቸዋል። ምክንያቱም ትናንሽ ኩባንያዎች የመለዋወጫ ዕቃዎችንና ሌሎችን አገልግሎቶች አቅራቢዎች ስለሆኑ ትላልቅ ኩባንያዎችም ሲዘጉ እነሱም አብረው ይጠቃሉ። መንግስት ሁሉንም ኩባንያዎችና የግለሰብ መደብሮችን ለመርዳት ለጊዜው በአገር ደረጃ 150 ቢሊዮን ኦይሮ ሲመድብ፣ ክፍለ-ሀገሮች ደግሞ እንደ የኢኮኖሚ አቅማቸው የተወሰነ የድጎማ በጀት መድበዋል። በዚህ ረገድ ተቀዳሚነቱን ቦታ የያዘው ባቬሪያ የሚባለው የበለጸገው የመኪናና የቴክኖሎጂ አምራች ክፍለ-ሀገር ነው። የአገሩ አስተዳደር 10 ቢሊዮን ኦይሮ ሲመድብ፣ የሃኪም ቤት ሰራተኞች ደግሞ ለመልካም ስራቸው ከቀረጥ ነፃ የሆነ 500 ኦይሮ ይሰጣቸዋል። ይህ ሁሉ ዕርዳታ በመደረግ ላይ እያለ ወደፊት ኢኮኖሚውን እንደገና ለማንቀሳቀስ እስከ 750 ቢሊዮን ኦይሮ መመደብ እንደሚያስፈልግ ይወራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የጣሊያንና የስፔይን መንግስታትም ከኮረና ቫይረስ ባኋላ ጠቅላላውን ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚል ሰፊ በጀት መድበዋል። የጣሊያን መንግስት 400 ቢሊዮን ኦይሮ ለመመደብ ሲዘጋጅ፣ የስፔይን መንግስት ደግሞ በተለይም ስራ ለሌለው ለእያንዳንዱ ዜጋ ለመኖር የሚያስችለው መሰረታዊ ገቢ(Basic Income) ተግባራዊ እንደሚያደርግ ቃል-ኪዳን ገብቷል። በሌላው ወገን ደግሞ እያንዳንዱ አገር ተግባራዊ ለማድረግ ካቀደው ውጭ የባቬሪያው የጀርመን ክፍለ-ሀገር አስተዳዳሪ የአውሮፓው አንድነት የማርሻል ፕላን ያስፈልገዋል በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የአውሮፓ መንግስታት ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚሰማቸውና ለሀገራቸውም እንደሚያስቡ ነው።

ከዚህ ውጭ ግን ለጊዜው ስራቸውን እንዲያቋርጡ የተገደዱ ሰራተኞች ወደ ስራ ቦታቸው እስኪመለሱ ድረስ መንግስት ልጅ ላለው ሰራተኛ 67% ከንጹህ ገቢው ሲከፍል፣ ልጅ ለሌለው ደግሞ 60% ይከፈለዋል። የክፍያ ጊዜውም 12 ወር ያህል ነው። ይህ ዐይነቱ የአጭር ጊዜ የስራ-አበል በመባል ይታወቃል። በዚህ መልክ ከሞላ ጎደል የሰራተኛው የመግዛት ኃይል ይጠበቃል። በስራ ሚኒስተር ስር የሚተዳደረው የስራ ቦታ አፈላላጊ መስሪያ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ፋብሪካዎች ሊዘጉ ይችላሉ ብሎ ስለሚያምን ሁልጊዜ መጠባበቂያ ገንዘብ ያስቀምጣል። ይህ ዐይነቱ የአጭር ጊዜ የስራ አበል ጠቅላላው ኢኮኖሚ እንዳይዳከም ያደርጋል። ምክንያቱም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የሰራተኛው የመግዛት ኃይል የተጠበቀ እንደሆን ብቻ ነው የተከማቹ ምግቦችም ሆነ በየጊዜው የሚቀርቡ ፍርፋሬዎች ሊሽጡ የሚችሉት። በዚህ መልክ በምርትና በፍጆታ መሀከል ያለው ግኑኝነት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ይጠበቃል። ማህበራዊ ቀውስም ወይም ግጭት እንዳይኖር ያደርጋል።

ወደ አጠቃላዩ አውሮፓ አንድነት አገሮች ሁኔታ ስንመጣ፣ በተለይም እንደ ጣሊያንና ፈረንሳይ የመሳሰሉት የኦይሮ አባል አገሮች የሚያነሱትና የሚወተውቱት በኮሮና ቫይረስ የደረሰውን የኢኮኖሚ ድክመት ለመቋቋምና እንደገና መልሶ ለመገንባት የኮሮና ወይም የኦይሮ ቦንድን እንደመያዣ በማቅረብ ከካፒታል ገበያ ገንዘብ መሰብሰና ኢንቬስት ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት በተለይም በጀርመን መንግስት ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም። ምክንያቱም የኮሮና ወይም የኦይሮ ቦንድ ሁሉንም የኦይሮ አባል አገሮች እንደ ባለዕዳ አድርጎ የሚወስድና እንደየኢኮኖሚ አቅማቸው ዕዳውን መልሰው የሚከፍሉ ስለሆነ የመጨረሻ መጨረሻ አብዛኛውን ዕዳ ጀርመን ትሸከማለች የሚል ፍርሃት አለ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከፍተኛ ተቃውሞ አለ። ይሁንና ከፍተኛ ግፊት ስላለ ጀርመን በዚህ የከረረ አቋሟ ትገፋ አትገፋ እንደሆን ከአሁኑ መናገር አይቻልም። ያለው ስምምነት ግን አፍጦ አግጦ ያለውን ችግር በጋራ መወጣት አለብን፣ ለዚህ ዐይነቱ ቀውጢ ቀን የማይደርስ የጋራ ገበያ ትርጉሙ የት ላይ ነው እየተባለ ነው የሚጠየቀው። በሌላ ወገን ግን የአውሮፓው አንድነት በተለይም በኮሮና የተጠቁ እንደ ጣሊያንና ስፔይን፣ እንዲሁም ፈረንሳይን የመሳሰሉ አገሮችን ለመርዳት 100 ቢሊዮን ኦይሮ እንደሚያቀርብ የኮሚሽኑ ፕሬዚደንት ጀርመናይቷ ወይዘሮ ፎን ደር ሌየን አስታውቀዋል። ይሁንና የአውሮፓው አንድነት መሪዎች በፕሬዚዳንቷ ሃሳብ መስማማት አለባቸው። እነሱ እሺ ሲሉና በህግ ሲጸድቅ ብቻ ነው ገንዘቡ የሚሰበሰበውና ለተጠቁት አገሮች የሚመደበው። የመስማማታቸው ጉዳይ የተረጋገጠ ለመሆኑ አንዳንድ ጋዜጠኞች ያወራሉ።

ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ የቫይረሱን መራባት ለመግታት ተብሎ የተወሰደው ሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂ ከኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ባሻገር ያስከተለው ሌላ ችግር አብዛኛው ሰው ቤቱ ውስጥ እንዲቀመጥ መገደዱ ነው። እንደሚታወቀው በተለይም ጸሀዩ ሞቅ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ሁሉም ወደ ወጭ ወጥቶ መናፈስና በየቡና ቤቶች እየገባ መብላትና መጠጣት ይፈልጋል። ይህ ዐይነቱ ውጭ መውጣትና መንሸራሸር፣ ምግብና መጠጥ ቤቶች ሂዶ መብላትና መጠጣት ባህልም ስለሆነ በየግለሰቦች ላይ አሉታዊ የስነ-ልቦና ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በተለይም እንደኳስ ሜዳዎች የመሳሰሉት በመዘጋታቸው አብዛኛውን ኳስ ጨዋታ ተመልካች ችግር ውስጥ ከትቶታል። እንደዚሁም ቲያትር ቤቶችና ሙዚየሞች የሚገባው ሰው፣ በተለይም በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች የዚህ ዐይነቱ የሁሉንም የመዝጋት ስትራቴጂ ስለባ ሆነዋል። ሌሎችም ተከታታይ ገቢ የሌላቸውና አልፎ አልፎ ልዩ ልዩ ዝግቶችን የሚያቀርቡ በጭንቀት ላይ ናቸው። ምክንያቱም መንግስት ለእያንዳንዱ ሊደረስ ስለማይችል ነው። አሁን ሰው በጉጉት የሚጠብቀውና የሚጠይቀው በተለይም ጀርመን አገር መቼ ነው ሁሉ ነገር ወደ ቀድሞው ሁኔታው የሚመለሰው? እያለ ነው። ግፊቱ ከመብዛቱ የተነሳ መንግስት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የወደቀ ይመስላል። ምናልባት ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ አንዳንድ የስራ መስኮችና የንግድ መደብሮች ቀስ በቀስ ሊከፈቱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ ወግን ግን የኮረና ቫይረስ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ጎንም እንዳለው አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ቻይናም ሆነ ጀርመን፣ እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የምርት ክንውን እንዲቋረጥ በመደረጉ አየሩ እየፀዳ መምጣት እንደቻለ ይነገራል። በመንገድ ላይም እንደወትሮው ብዙ መኪና ስለማይታይ ንጹህ አየር መተንፈስ ተችሏል። በተጨማሪም ከሚታየው ጭንቀት ባሻገር አብዛኛው ህዝብ ከዚህ ቀደም ይኖርና ይሰራ እንደነበረው ሁኔታው መቀጠል እንደማይችል በመወያየት ላይ ነው። የአመጋገብና የአሰራር ባህላችን መለወጥ አለባቸው በማለት በተለይም ለተከታዩ ትውልድ ያስባል። ባለፉት ሰላሳ ዐመታት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ጥሬ-ሀብትን መቆጠብና የአካባቢን ሁኔታ ማሻሻል አልተቻለም። በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ማድረግ የተነሳም በሰራተኛው ላይ ያለው የስራ ጭነት በፍጹም አልቀነሰም።

ኮሮና ቫይረስን አሳቦ የዓለምን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር አዝማሚያ!

ይህንን ዐይነቱን ሁኔታ ተጠቅመው ዓለም አቀፋዊ አገዛዝን ለማምጣት(World Governance) ወይም ያለውን ለማጠናከር የሚሯሯጡ ኃይሎች እንዳሉ ግልጽ ነው። በተለይም እንደ ቢል ጌት የመሳሰሉት በፋውንዴሽኑ አማካይነት የዓለም ጤና ድርጅቱን(WHO) ወደ 400 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ የዓመት ባጅት በመመደብ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የታወቀ ነው። የፋርማሲ ኢንዱስትሪዎችና እንደዚሁም የአውሮፓው አንድነት ለጤና ድርጅቱ ከፍተኛ ባጀት በድምር እስከ 800 ቢሊዮን ኦይሮ ይከፍላሉ። እነዚህ በራሳቸው ደግሞ ከትላልቅ የገንዘብ ድርጅቶችና ባንኮች ጋር የተቆላለፉ ናቸው። ይህም ማለት የጤና ድርጅቱ በበጀቱ የሚመካው በአባል አገሮቹ ሳይሆን በእንደነዚህ ዐይነቶች የዓለምን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል በሚወስኑ ትላልቅ ኩባንያዎችና ፋውንዴሽኖች አማካይነት ነው ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው ሳርስ የተባለው ቫይረስ በተከሰተበት ወቅት የጤና ድርጅቱ ወረርሽኝ ተከስቷል በማለት ቀደም ብሎ ያወጀውና ብዙ አገሮችን ለማሳሳት የበቃው። በጊዜው የክትባት መድሃኒት እንዲመረት ቢደረግም እንደተወራው ወረርሽኙ ሳይከሰት ቀርቷል። የተመረተው ምርትም ጥቅም ላይ ባይውልም የፋርማሲ ኢንዱስትሪዎች ግን የትርፍ ትርፍ አግኝተዋል። ይህ ጉዳይ በብዙ ሀኪሞች ተተችቷል።

ይህ የሚያመለክተው ምንድነው? እንደ ቢል ጌት የመሳሰሉት በሀብት የናጠጡ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በፋርማሲ ኢንዱስትሪና የዘር ማዳበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ስላላቸው ይህንን ተጠቅመው የክትባት መድሃኒት እንዲመረት ከፍተኛ ግፊት ያደርጋሉ። በዚህም መሰረት አንድ ቀን እሱም ሆነ ሌሎች ድርሻ ያላቸውና የየኩባንያዎቹ ማናጄሮች ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት ገቢያቸውን ያሳድጋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የፋርማሲ ኢንዱስትሪ በየዓመት የሚያገኘው ትርፍ አልበቃ ስላለው በሳይንስ ያልተመረመሩና ደረጃዎችን የጠበቁ አይደሉም እያለ እየተከታተለ ባህላዊ የሚባሉ መድሃኒቶችን የሚሸጡ መደብሮች እንዲዘጉ ለማድረግ በቅቷል። ከአርባ ዐመት በላይ ለህዝብ ግልጋሎት ይሰጡ የነበሩና በተለይም በዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች እየሄዱ የሚገዙባቸው የባህል መድሃኒት መሸጫ መደብሮች በተለይም በቅጠል መልክ የሚሸጡና እንደ ሻይ የሚጠጡ በህግ ትዕዛዝ እንዲዘጉ ተደርገዋል። በጀርመን አገር አማራጭ መድሃኒቶች የሚሸጡባቸው መደብሮች በህግ የተፈቀዱ ነበሩ። እንዲዘጉ እስከተደረጉበት ጊዜ ድረስም መድሃኒቶቹ በሙሉ በሰው ላይ አደጋ አስከትለዋል ተብሎ አንድም ቀን ተመዝግቦ አያውቅም። ያም ሆነ ይህ የእነ ቢል ጌትና የተለያዩ የፋርማሲ ኢንዱስትሪዎች መቆላለፍ አንደ ኮረና ቫይረስ የመሳሰሉ ወረርሽኞት በሚከሰቱበት ጊዜ ይህንን በማሳበብ የክትባት መድሃኒቶች ለማምረት ይሯሯጣሉ። በዚህም አማካይነት የብዙ ሚሊያርድን ህዝብ ጤንነት ይቆጣጠራሉ፤ የመኖርና ያለመኖር ዕድልም ይወስናሉ። በተለይም በጥቅም የተገዙ የፖለቲካ ኤሊቶችንና አገዛዞችን በመጠቀም በአፍሪካ ምድር በምስኪኑ ወጣት ላይ በተለይም በሴቶች ላይ የተለያዩ የክትባት መድሃኒቶችን ሙከራ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ዩኒሴፍ ከዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅቱ ጋር በመተባበር የቴታነስ ክትባት ለማድረግ በ2013 ዓ.ም ከኬንያ መንግስት ፈቃድ በማግኘትና ሃኪሞቹ በወታደር በመታጀብ በወጣት ሴቶች ላይ የክትባት ሙከራ ያደርጋሉ። ለምንድነው በወጣት ሴቶች ላይ ብቻ ይህ ዐይነቱ ክትባት የሚደረገው? ብለው ተቃውሞ ያነሱ ቄሶች በታጠቁ ወታደሮች እንዲበተኑ ያደርጋሉ። የኋላ ኋላ ለቴታነስ ተብሎ የቀረበው የክትባት መድሃኒት ሲመረመር ወጣት ሴትች እንዳያረግዙ የሚያመክን መድሃኒት መሆኑ ይድረስበታል። ወደ ኢትዮጵያችንም ስንመጣ እነ አቶ መለስ ዜናዊ ከአሜሪካን መንግስትና ከእነቢል ጌት ጋር እጅና ጓንቲ ሆነው አብረው በሚሰሩበት ዘመን በአማራው ክልል ውስጥ ወጣት ሴቶች እንዳያረግዙ የሚያደርግ የክትባት መድሃኒት ይወጉ እንደነበር በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። አሁን ደግሞ እነቢል ጌት የኮረና ቫይረስን አሳበው ህዝብን በፍርሃት እንዲዋጥ ካደረጉ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠቅላላው የዓለም ህዝብ መከተብ አለበት እያሉ ያስወራሉ። በተለይም በአፍሪካ ህዝብ ላይ ሙከራ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ጀምራዋል። መንግስታችንም ሆነ ጠቅላላው ህዝብ በኮረና ቫይረስ መደናገጥ የለበትም። አማራጭ ዘዴዎችን መፈለግ አለበት። ለማንኛውም እንደዚህ ዐይነቱን ወንጀል እየተከታተለ የሚያጠናና የሚቃወም በቤተክርስቲያንም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የነቃና የተደራጀ የሲቭል ማህበረሰብ መኖር አስፈላጊ ነው። ነገሮችን በጥብቅ መከታተልና በነቃ መንፈስ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን መሰብሰብና ለህዝብ ማዳረስ ያስፈልጋል። በቀላሉ የውጭ አማካሪዎች በሚባሉ እንዳንታለል ኃላፊነትን የሚጠይቅ ስራ መስራት አለብን።

ወደ ባንኮችና ፋይናስ ገበያ ስንመጣ ደግሞ በወረቀት ገንዘብና በሳንቲሞች ላይ የተሳሳተ ወሬ በመንዛት ወይም በማስፋፋት የወረቀት ገንዘብም ሆነ ሳንቲሞች የመገበያያ መሳሪያዎች መሆናቸውን እንዲያቆሙ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው። እንደሚያስወሩት ከሆነ የወረቀት ገንዘብና ሳንቲሞች እንደ ኮረና ቫይረስ የመሳሰሉትን የማስፋፋት ኃይላቸው ከፍተኛ ነው። ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ በተደረገ ጥናት መሰረት በሁለቱም የመገበያያ መሳሪያዎች አማካይነት ቫይረሱ የመተላለፍ ኃይሉ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው። የጀርመን ማዕከላዊ ባንክ ከአስር ቀን በፊት ባደረገው ስብሰባ ይህን ዐይነቱን ከአሜሪካ ባንኮች የሚመጣውን ግፊት ውድቅ በማድረግ የወረቀት ገንዘብና ሳንቲሞችን ከመጠቀም ፈቀቅ እንደማይል አስታውቋል። በባንኩም ዋና አስተዳዳሪ ዕምነት የወረቀት ገንዘብንና ሳንቲምን መጠቀም እንደ ባህል የተወሰዱና የነፃነት ምልክቶችም ሆነው ስለሚታዩ የጀርመን ህዝብ አይቀበለውም በማለት በግልጽ ይናገራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይም በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ አብዛኛውን ጊዜ ገንዘባቸውን ከፍራሻቸው በታች ነው የሚያስቀምጡት። ስለሆነም ይህ ዐይነት አዝማሚያ በጀርመን ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ምናልባትም ከዚህ ጋር በተያያዘና በኮረና ቫይረሱ ጋር በተያያዘ ግፊት የተነሳ የአንድ ክፍለ-ሀገር የፊናንስ ሚኒስተር-ሄሰን ተብሎ የሚጠራው የጀርመን ክፍለ-ሀገር- የክርስቲያን ዲሞክራቲክ አባል የሆነ እራሱን ገድሏል ተብሎ ተወርቷል። የክፍለ-ሀገሩ አስተዳዳሪና ጓደኛቸው የሆኑት መሪም ይህንን በማረጋገጥ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

ያም ሆነ ይህ እንደ ክሬዲት ካርድ የመሳሰሉት የተለያየ ስም ያላቸው የመግዣ ወይም የመገበያያ መሳሪያዎች በየአገሩ ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ ዋናው ተጠቃሚው ይህንን የፕላስቲክ ገንዘብ የሚያትሙ ትላልቅ የአሜሪካን ኩባንያዎች ብቻ ናቸው። አንድ ሰው ገንዘብ ባወጣና በከፈለ ቁጥር የግዴታ ግብር መክፈል ሳለለበት በግብሩ ትርፍ ያካብታሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ዐይነቱ የመገበያያ መሳሪያ አማካይነት የየግለሰቦችን የአመጋገብ ባህርይ፣ የት የት ቦታ አንድ ሰው ምግብና ሌሎች ነገሮችን እንደገዛ፣ የት የት መጠጥ ቤቶችና መዝናኛ ቦታዎች ገብቶ እንደሚመገብና እንደሚዝናናም ማወቅ ይችላሉ። በዚህ አማካይነትም በተለይም አደገኛ የሚባሉ ሰዎችን ማስወገድ ይቻላል። የፕላስቲክ ገንዘብን እንቀበል ብንል እንኳ ይህ ዐይነቱ የአከፋፈል ዘዴ ተከታታይ ገቢ ላለው ሰው ብቻ ነው የሚጠቅመው። ተከታታይ ገቢ የሌለው ወይም መንገድ ላይ ተቀምጦ የሚለምን፣ ወይም በሜትሮ መግቢያና መውጫው ላይ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ጊታር የሚጫወት፣ ወይም ሰው በሚዘዋወርበት ቦታ ልዩ አክሮባት የሚሰራና በዚህም አማካይነት የተወሰነ ገንዘብ ለማግኘት የሚፈልግ፣ በየቦታው ተቀምጠው ስዕል የሚሰሩ ሁሉ ሙሉ በሙሉ የፕላስቲክ ገንዘብ ተግባራዊ ከሆነ ምንም ዐይነት ገቢ ሊያገኙ አይችሉም ማለት ነው። ይህም ማለት የባሰውኑ ወደ ድህነትና ርሃብ ይወረወራሉ። በተጨማሪም ሽማግሌ ሴቶችም ሆነ ወንዶች ከወረቀት ገንዘብ ጋር ልዩ ዐይነት ግኑኝነት ያላቸው ስለሆነና ከዕድሜ ብዛትም ጋር በተያያዘ የክሬዲት ካርዳቸውን ቁጥር ስለሚረሱም እነዚህም በዚህ ዐይነቱ የአከፋፈል ዘዴ የሚጠቁ ናቸው። በመሆኑም ይህ ዐይነቱ የእነቢል ጌትና የትላልቅ የአሜሪካ ባንኮች አካሄድ በጣም አደገኛ በመሆኑ የእነሱን ግፊት መቋቋም ያስፈልጋል። በክሬዲት ካርድ መክፈልም የስልጣኔ ምልክት ሆኖ መታየት የለበትም። በሌላ ወገን ግን አንድ ሰው ከአገሩ ወደ ሌላ አገር ዕቃዎችን ለመግዛትም ሆነ ለጉብኝት ወይም ደግሞ ለስራ ጉዳይ የሚሄድ ከሆነ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ መዘዋወር ስለማይችል የግዴታ ክሬዲት ካርድን መጠቀሙ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል። ስለሆነም የወረቀት ገንዘብም ሆነ የክሬዲት ካርዶች ጎን ለጎን መሄድ ያለባቸው የመገበያያ መሳሪያዎች እንጂ አንዱ ሙሉ በሙሉ እንዳለ በሌላኛው የሚተካበት ምክንያት የለም።

በተለይም ይህ ጉዳይ በኢኮኖሚያቸው ወደ ኋላ በቀሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ግልጽ መሆን አለበት። ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ህዝብ በገጠር ውስጥ በሚኖርበት አገርና፣ ገና የምርት ክንዋኔ ባልተስፋፋበት፣ እንዲሁም ደግሞ የውስጥ ገበያ ባልዳበረበት አገር የፕላስቲክ የመገበያያ መሳሪያን ተግባራዊ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚው እንዳያድግም ትልቅ ማነቆ እንደመፍጠር ይቆጠራል። ማንኛውም ነገር ሁኔታዎችን ተከትሎ ማደግ አለበት። የምርት ክንውን ሲስፋፋ፣ ቴክኖሎጂዎች ሲዳብሩና የገንዘብ ልውውጥ በባንኮች አማካይነት ከአንድ ግለሰብ እጅ ወደ ሌላኛው እጅ የሚተላለፍ ከሆነ በከፊል የክሬዲት ሲይስተምን ማስገባት ወይም ማለማመድ ይቻላል። ለማንኛውም ካፒታሊዝም ባላደገበት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት፣ የተለያዩ የአመራረት ግኑኝነቶች እዚያው በዚያ በሚገኙበትና በተለያዩ መስኮች ዘንድ ውስጣዊ ግኑኝነት በሌለበት አገር ክሬዲት ካርድን የመገበያያ መሳሪያ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ግልጽ የስራ ክፍፍል ሲኖርና በተለያዩ የምርት መስኮች መሀከል በመግዛትና በመሸጥ መሀከል ግኑኝነት የሚፈጠር ከሆነ በክሬዲት ካርድ ብቻ ሳይሆን በሌላ ጥሬ ገንዘብ ባልሆነም መገበያየት ይቻላል።

ለማንኛውም ቀድሞም ሆነ አሁን ደግሞ ይህንን ዐይነቱን ወረርሽኝ በመጠቀም የዓለምን የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ሰብሎችን ለመቆጣጠር የሚሯሯጡት ትላልቅ የአሜሪካ የገንዘብ አስተዳዳሪዎችና(Hedge Funds) እራሱ የአሜሪካ መንግስትም የዓለምን ህዝብ እንደፈለግነው ማሽከርከር እንችላለን በማለት ያስፈራራሉ። የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሄር አምሳል ነው የተፈጠረው የሚለውን የመጽሀፍ ቅዱስ አባባል በመጣስ በዓለም ህዝብ ላይ የራሳቸውን የበላይነት ጭነዋል። ከዚህም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባህላዊና በቤተሰብ የሚተዳደሩና ብዙ ፈጠራም የሚካሄድባቸውን ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በአሜሪካን የገንዘብ አስተዳዳሪዎችና ባንኮች እየተገዙ ትርፋማ በሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያተኮሩ በማድረግ እየተዳከሙ ነው። የማምረቻን ዋጋ ለመቀነስ በማለት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞች ከስራቸው ይባረራሉ። ረጋ ያለና የተስተካከለና ሚዛናዊነት ያለው የኢንዱስትሪ ተከላ ለማካሄድ ሳይሆን ገንዘብን በገንዘብ ለማትረፍ በሚለው ስትራቲጂ የሚደረገው እሽቅድምድሞሽ ራሳቸው ኢንዱስትሪ አገሮችንም እያዳከማቸው ነው። ይህንና በአጠቃላይ ሲታይ የነፃ ገበያን(Free Trade) አስመልክቶ የራሽያው ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲንና የቱርኩ ፕሬዚደንት ሬሴፕ ቴይፕ ኤርዶጋን ከኮራን ቫይረስ ማክተም ወይም ማግስት በኋላ የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ በድሮው መልካቸው መቀጠል እንደማይችሉ በግልጽ ተናግረዋል። በእነሱ አባባልም ሁሉም አገር በመጀመሪያ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ነገር የአገሩን ኢኮኖሚ መገንባትና ለየራሱ ህዝብ አስተማማኝ ሁኔታን መፍጠር ነው። በፕሬዚደንት ኤርዶጋን አባባልም አንድ መንግስት ሊኖር ወይም ሊጠነክር የሚችለው በየአገሩ ያለ ህዝብ በሰላም ሲኖርና የማምረት ኃይሉ ሲዳብር ብቻ ነው። ስለሆነም ይላሉ፣ የእያንዳንዱ አገር ህዝብ በሰላም እንዲኖር መተው አለብን። ገንዘብና የኩባንያዎች ድርሻ የሰውን ልጅ ዕድል መወሰን እንደሌለባቸው በግልጽ ተናግረዋል። ይህ ዐይነቱ አባባል የአሜሪካንን ሄጅ ፈንድ አስተዳዳሪዎችንና በከፍተኛ ደረጃ የዓለምን ህዝብ ነፃነት የሚጋፋውንና በሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ የሚደገፈውን የአሜሪካን ኢምፔሬያሊዝምን የሚዋጥለት አይደለም።

ይህ ዐይነቱን የተወሳሰበና የግሎባል ካፒታሊዝም ተዋንያን የሚያደርጉትን ግፊት አስመልክቶ በተለይም በካፒታሊስ አገሮች ውይይት ይደረጋል። በአብዛኛዎች ተመራማሪዎች አስተያየት ካፒታሊዝም እስካሁን በሄደበት መንገድ ወደፊት መቀጠል እንደማይችል በግልጽ ይናገራሉ። በተለይም በሰባኛው ዓ.ም የኢኮኖሚ ዕድገት ገደብነትን(The Limits of Growth) አስመልክቶ ሮም ላይ በተሰበስቡ የኢኮኖሚ ሊሂቃን በቀረበው ጥናት መሰረት በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ እየሆነ መጥቷል። ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ጎተ የሚባለው የጀርመኑ ፈላስፋ፣ ገጣሚና ሳይንቲስት በ19ኛ ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ፋውስት በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ዛፍ እስከሰማይ ድረስ ለማደግ አይችልም በማለት የኢኮኖሚ ዕድገት ገደብነትን አመልክቷል። በተለይም ኢኮኖሚ ከባህል ስር መሆን እንዳለበትና የሰው ልጅም መንፈስ በገንዘብ እንዳይበረዝ ስነ-ምግባርን የተከተለ የአመራረት ዘዴና የንግድ ልውውጥ መኖር ለሰው ልጅ ተስማምቶ መኖር አስፈላጊ መሆናቸውን ከጥንቱ የመጀመሪያዎቹ ፈላስፋዎች ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍል-ዘመን ድረስ እንደመመሪያ ተሰብኳል። በእነዚህ ፈላስፋዎችም ሆነ በዘመኑ የስነ-ምግባር አስተማሪዎች አመለካከትና ዕምነት ማንኛውም ነገር ገደብ እንዲኖረው ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ግለሰብም እስከምን ድረስ መሄድ እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል። ለማንኛውም በአብዛኛዎቹ ትችታዊ አመለካከት ባላቸው የተፈጥሮም ሆነ የሶሻል ሳይንቲስቶችና የኢኮሎጂ ተመራማሪዎች የሚነሳው ጥያቄ የሚመረቱት ምርቶች በሙሉ የሰው ልጅ ሊጠቀም ከሚችለው በላይ ናቸው። በተጨማሪም ተፈጥሮ ይህንን ዐይነቱን የአስተራረስና የአመራረት ዘዴ ልትሸከመው እንደማትችል በየጊዜው የሚታየው ቀውስ ያረጋግጣል። በተለይም በካርቦን ዳይ ኦክሳይድና በሌሎች ከኢንዱስትሪና ከመኪና በሚወጡ መርዞች የተነሳ የተፈጥሮ ሚዛናዊነት እየተናጋ ነው። የረጉና ለመሬት ጥርበት የሚጠቅሙ በረዶዎች በአየሩ ሙቀት የተነሳ እየቀለጡ ነው። ከዚህም በላይ በኢንዱስትሪ በተደገፈ የአስተራረስ ዘዴና የማዳበሪያና የተባይ ማጥፊያዎች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በመሬት ውስጥ የሚገኘው ውሃ መበከሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለአዕፅዋት አስፈላጊ የሆኑ ኢንሴክቶችና ለተለያዩ ሰብሎች ጣዕምን የምትለግሰው እንደ ንብ የመሳሰሉት ጠቃሚ ህይወት ያላቸው በራሪ ነገሮች በቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱ ሊመጡ ችለዋል። ስለሆነም ይላሉ እነዚህ ተመራማሪዎችና ተቆርቋሪዎች፣ ይህ ዐይነቱ በተፈጥሮ ላይ የሚደረገው ግፊትና አላስፈላጊ ብዝባዛ የተፈጥሮን ሁኔታ አናግቶታል። በተለይም ባይከቴሪያዎች ከአዳዲስ መድሃኒቶች ጋር ስለሚለማመዱ በየጊዜው በሚመረትና በሚሰራጭ መድሃኒት በቀላሉ ሊወገዱ ስለማይችሉ የተለያዩ የተባይ ማጥፊያዎችን ማምረትምና በሰብል ላይ ማሰራጨት አካባቢን ከማውደምና አስፈላጊ ተባዮችን ከመግደል በስተቀር አዎንታዊ ውጤቱ እዚህ ግባ የሚባል እንዳይደለ ይናገራሉ ። ስለሆነም የዓለም ህዝብ በእንደዚህ ዐይነቱ አኗኗር ዘዴ ወደፊት ለመግፋት እንደማይችልና፣ በተፈጥሮና በሰው መሀከል ያለው ግኑኝነት በመተሳሰብ ላይ እንዲመሰረትና-የሰው ልጅ ተፈጥሮን ይፈልጋታል እንጂ ተፈጥሮ ሰውን አትፈልገውም- ተከታታይነት ያለው የአስተራረስና የአመራረት ዘዴ አስፈላጊ ነው ብለው የሚያስተምሩና ግፊትም የሚያደርጉ ጥቂት አይደሉም። ስለሆነም ወደፊት የሚደረገው ትግል በዚህ ዐይነቱ ዙሪያ ይሆናል ማለት ነው። የሰው ልጅም የመማር ችሎታ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።

ኮረና ቫይረስና የአገራችንና የሌሎች አፍሪካ አገሮች ዕጣ!

ሰሞኑን በተለይም በውጭው ዓለም በሚኖረው ኢትዮጵያዊም ሆነ በአንዳንድ ለአፍሪካ በሚቆረቆሩ ፈረንጆች የሚወራው ነገር ቫይረሱ ልክ አሜሪካና አውሮፓ እንደታየው አፍሪካ ውስጥ በፍጥነት የሚስፋፋ ከሆነ ከፍተኛ ዕልቂት እንደሚያስከትል ነው። የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የአብዛኛዎችን አፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚዎች በአንጀት አጥብቅ ወይንም በኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ አማካይነት የሚያፈራርሰው የዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ቫይረሱ አፍሪካ ውስጥ ከተስፋፋ ሊያደርስ የሚችለውን ዕልቂት „በመጨነቅ“ ተናግረዋል።

የአፍሪካን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው አባዛኛዎች አገሮች፣ በተለይም ዋና ከተማዎችና ሌሎች ትላልቅ የሚባሉ ከተማዎች በዕቅድ የተገነቡ አይደሉም። በከተማዎች ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ አብዛኛው የቆሻሻ መኖሪያዎች(Slums) ቦታ ነው የሚኖረው። ለምሳሌ በናይሮቢ ከተማ ከሚኖረው ጠቅላላ ህዝብ ከ65-70% የሚሆነው በቆሻሻ ቦታዎች የሚኖር ነው። አዲስ አበባና ሌጎስ እንዲሁም ጆሃንስ በርግ ተመሳሳይ ሁኔታ እናያለን። በከተማችን ውስጥ 80% የሚሆነው ህዝብ በቆሻሻ ቦታ ነው የሚኖረው። በመጸዳጃ ቦታዎች እጥረትና በንጹህ ውሃ በበቂው አለመገኘት ምክንያትና፣ ቆሻሻዎችም ዝም ብለው በየቦታው ስለሚጣሉና ስለሚደፉ ወይም ስለሚከማቹ በከተማዎች የሚኖረው ህዝብ ለበሽታ የተጋለጠ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥም ከሶስትና አራት በላይ ሰዎች ተጨናንቀው ይኖራሉ። በየጊቢውም የመጸዳጃ ቦታ የለም። ይህ ጉዳይና በበቂው ሆስፒታሎች ወይም ክሊኒኮች አለመኖራቸው የአፍሪካን ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል። በተጨማሪም የመገበያያ ቦታዎች በስርዓት የተዘጋጁና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጋፉ የሚገበያዩባቸው ናቸው። በዚህ ዐይነቱ ውጥንቅጡ በወጣ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ተራርቃችሁ ሂዱ ወይም ተቀመጡ(Social Distancing) ማለት በምድር ላይ በግልጽ የሚታየውን ነገር በደንብ አለመገንዘብ ይቆጠራል። ከዚህም በላይ አብዛኛው ህዝብ ቋሚ ስራ የሌለውና ኢንፎርማል መስክ በሚባለው የሚሰራ ነው። ለምሳሌ 80% የሚሆነው የናይሮቢ ኗሪ ህዝብ በኢንፎርማል መስክ እየሰራ የሚተዳደር ነው። ይህም ማለት አብዛኛው ህዝብ ተከታታይ የሆነ ገቢ የለውም ማለት ነው። ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የሚኖርን ህዝብ ቤትህ ውስጥ ተቀመጥ ማለት እንደ ቅብጠተና እንደ ቅጣት የሚቆጠር እንጂ ለህዝብ እንደማሰብ የሚቆጠር አይደለም። ለብዙ ሳምንታትም ሆነ ለወራት ምን እየበላና ለኪራይ ቤትም ምን እንደሚከፍል ለአፍሪካ መንግስታት ግልጽ የሆነ አይደለም። በተለይም አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት የሚወስዱት እርምጃ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ነው። ለምሳሌ ጆሃንስ በርግ በቆሻሻ መኖሪያ ቦታ የሚኖሩ ሰዎችን ወታደሩ ተራርቃችሁ ሂዱ እያለ በህዝብ ላይ ይተኩሳል። ስለሆነም በዚያ የሚኖረው ሰው የሚለው ኮሮናን ሳይሆን ስናይፐር ታጥቆ የሚመጣውንና በጭፍን የሚተኩስብንን ነው የምንፈራው እያለ ነው ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያሰማው።

የአገራችንንም ሆነ የጠቅላላውን አፍሪካ አገሮች ችግር ለመረዳት አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን ጠጋ ብለን እንመልከት። በየአገሩ ያሉትን የመንግስታት አወቃቀር ስንመለከት በሚሊታሪና በፀጥታ ኃይል ከመፈርጠም በስተቀር ህዞቦቻቸውን በየፊናው የሚያደራጁና ህብረተሰቡ በስነ-ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ምሁራዊ ኃይልና ብቃት ያላቸው አይደሉም። የተገለጸላቸውና ዘመናዊም አይደሉም። ስለሆነም የየመንግስታቱን መኪና በሚቆጣጠሩና በተቀረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቲ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን በህዝቡ መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኝነት የለም። በአንፃሩ የየአገሩ መንግስታት የውጭ መንግስታት ተጠሪዎችና ታዛዦች የሚመስሉና ህዝብን በማስፈራራት የሚኖሩ ናቸው እንጂ አገሮቻቸውን የሚወክሉ አይደሉም። ይህ ዐይነቱ የመንግስት አወቃቀርና ሰፋ ያለ ተቆርቋሪ የሆነ የሲቪል ማህበረሰብ አለመኖር እንደዚህ ዐይነት አስከፊ ቫይረስ በሚከሰትበትና በሚራባበት ጊዜ ሁኔታውን በፍጥነትና በቀላሉ ለመቆጣጠር አይቻልም።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአለፉት አርባና ሃምሳ ዐመታት አብዛኛዎች የአፍሪካ መንግስታት፣ አገራችንንም ጨምሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲያወጡና ተግባራዊ ሲያደርጉ ፖሊሲው አንድን አገር ሁለመንታዊ በሆነ መልክ እንዲገነባ የሚያደርግ ሳይሆን የሚያዳክምና አብዛኛውንም ህዝብ ወደ አንድ አቅጣጭ ብቻ እንዲያመራ የሚያደርግ ነው። 1ኛ) የሚቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በአንድ አካባቢ ወይም በዋና ዋና ከተሞች ነው። ይህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ አተካከል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አንድ ከተማ እንዲፈልሱ ያደርጋል። 2ኛ) የሚቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች የመባዛትና የማደግ፣ እንዲሁም ወደ ተለያየ አካባቢ የመሰራጨት ኃይል የላቸውም። 3ኛ) በአብዛኛዎች የአፍሪካ መንግስታት ዘንድ የማሺን ኢንዱስትሪና ፋይን ሜካኒክ የሚባሉ ነገሮች፣ በተለይም ለቴክኖሎጂ ዕድገትና ልዩ ልዩ የማምረቻ መሳሪያዎችን ለማምረት የሚያገለግሉ በሚገባ አይታወቁም። መንግስታትም ደንታ የላቸውም። 4ኛ) በየቦታው የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ጣቢያዎች የሉም። ዩኒቨርሲቲዎችም በዚህ መልክ አልተደራጁም። ለምሳሌ አውሮፓም ሆነ አሜሪካ መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ምርምሮች(Basic Research) የሚካሄዱት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጠው ትምህርት በቀለም ላይ ያተኮረ እንጂ የህብረተስቡን ችግር ሊፈታ ተብሎ አይደለም። 5ኛ) በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፈው አብዛኛው በንግድና በተቀሩት የአገልግሎት መስጫዎች ላይ እንጂ ህዝባዊ ወይም ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥሩ በሚችሉና ሰፋ ያለ የስራ-መስክ በሚከፍቱ ኢንዱስትሪዎች ላይ አይደለም። አብዛኛውም ነጋዴ ገንዘብ ለማግኘት ብሎ የሚነግድ እንጂ የፈጣሪ-መንፈስ(Pioneer Spirit) ያለውና ሪስክ በመውሰድ በቴክኖሎጂ ተከላ ላይ ለመሰማራት የሚጥር አይደለም። ገንዘብ ያለው ሆቴል ቤቶችን በመሰራት ለሀብረተሰቡ መዳረስ የሚገባቸውን እንደ ንፁህ ውሃና መብራት የሚጋራ ነው። የሚሰሩት ሆቴል ቤቶች ከህዝብ ፍላጎትና ከሪሶርስ ጋር እየተመጣጠኑ አይደለም። 6ኛ) በዚህም ምክንያት የተነሳ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ የማዕከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የሉም። 7ኛ) በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች አብዛኛው ህዝብ ኢንፎርማል መስክ በሚባለውና ከእጅ ወደ አፍ ተብሎ በሚጠራው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተደግፎ የሚኖር ነው። 8ኛ) ሰለሆነም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ያለው ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር እንደዚህ ነው ብሎ መናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። 9ኛ) በዚህ ዐይነት ግልጽነት የሌለው ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ላይ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና በእነ ዓለም ባንክ የሚደገፍ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ሁኔታውን ግልጽ ከማድረግ ይልቅ የባሰውኑ ያዘበራርቀዋል። ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ዘራፊ የሆኑ ኃይሎችን በመፍጠር በከፍተኛ ደረጃም አካባቢ እንዲወድም ያደርጋል። በየከተማዎች ያለውን በልዩ ልዩ መልክ የሚታየውን ቆሻሻ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለጤንነት አደገኛ የሆኑ ልዩ ልዩ ማዕድኖችና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በየቦታው እየተጣሉ በተለይም ወጣቱን ለአደጋ እያጋለጡት ነው። 10ኛ) በየክፍለ-ሀገሮች ከተማዎችም ሆነ ወረዳዎች ለህዝቡ ግልጋሎት የሚሰጡ ልዩ ልዩ ተቋማት የሉም። 11ኛ) በየአገሮች ውስጥ በሰፈነው ደካማ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እንስቃሴ አማካይነት የየመንግስታትም ገቢ በጣም ደካማ ነው። ስለሆነም መንግስታትና በየክፍለ-ሀገሮች ያሉት አስተዳዳሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለሰፊው ህዝብ ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ ክሊኒኮችን ሊገነቡ አይችሉም። በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የየመንግስታትና የሎካል አስተዳዳሪዎች ሚና የግዴታ ወደ ጦርነትና ህዝብን ወደ ማስፈራራት ያዘነብላል። በተለይም የአገራችን ሁኔታ የሚያረጋግጠው አገሪቱ ወደ ጦር ቀጠናነት የተለወጠች ነው የሚመስለው።

የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ስንመለከት ባለፉት 28 ዐመታት ተግባራዊ የሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ ለዘረፋ የሚያመቹና የተወሰነውን ህብረተሰብ ክፍል የሚያደልቡ ናቸው። አንድ አገር በስኳር ተከላና በስኳር ፋብሪካ ትበለጽግ ይመስል የህወሃት አገዛዝ ብዙ ሀብት በዚህ መስክ እንዲፈስና ሙስናም እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅቷል። ለአገር ውስጥ ገበያ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ተብለው አትኩሮ የተሰጣቸው የእርሻ ምርት ውጤቶች ለቴክኖሎጂ ዕድገት አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ አይደሉም። በህዳሴው ግድብ ላይ የተደረገውና የሚደረገው ርብርቦሽ የማያስፈልግና በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰበት ነው። በዚያ ላይ የፈሰሰውን ገንዘብ በቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ቢውልና አነሰተኛና ለማስተዳደር የሚያስችሉ ግድቦች በየቦታው ቢገነቡ ኖሮ እንደዚህ ዐይነት የሆነ ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ባልገባን ነበር። በእልክ ላይና በአወቅኹኝ ባይነት፣ እንዲሁም ጠቅላላውን ኢትዮጵያ ሳይሆን የትግራይን ክልል በኢንዱስትሪ ለማብለጸግና እንዲሁም ኃይል ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ ታስቦ የታቀደውና የሚገነባው ህዳሴ ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ የከተተን ብቻ ሳይሆን አላስፈላጊ አርቲፊሻል የሆነ የአገር ስሜት ውስጥ ከቶናል። ይህንን ትተን የከተማዎችን፣ በተለይም የአዲስ አበባን በህዝብ መጨናነቅ ስንመለከት ህወሃትና የኦሮሞ ነፃነት ድርጅት(OLF) አንድ ላይ ሆነው አገሪቱን „በሚያስተዳድሩበት“ ዘመን የተከተሉት ህዝብን የማፈናቀል ፖሊሲ በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ለህይወታቸው የፈሩ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ አማራዎችና ጉራጌዎች፣ እንዲሁም የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ወደ አዲስ አበባ ፈልሰው ከተማይቱን ለማጨናነቅ በቅተዋል። ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ ደግሞ በዶ/ር አቢይ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ(ODP) ስልጣንን ከጨበጠ ወዲህ ሁኔታውን ለመጠቀም የፈለጉ የድርጅቱ አባሎችም ሆነ ኦነግ ከሀረር ተፈናቀሉ የተባሉ ኦሮሞዎችን አዲስ አበባና አካባቢው መጥተው እንዲሰፍሩ አድርገዋል። ይህ ሁኔታ የባስውኑ ዋና ከተማዋና ማጨናነቁ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ይኖር የነበረው ሰው በፍርሃት እንዲዋጥ ተደርጓል። በዚህ ላይ ይህን የመሰለ የወረርሽኝ በሽታ ሲስፋፋ የወረርሽኙን መስፋፋት ለማገድ በጣም ያስቸግራል።

ከላይ ከተዘረዘሩት ሁኔታዎች ስንነሳ የአገራችንም ሆነ የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ችግር በገንዘብ ስብሰባ የሚፈታ አይደለም። ወይም ደግሞ በውጭ ርዳታ መስመር የሚይዝ አይደለም። ችግሩ ውስብስብና ስር የሰደደ ከጭንቅላት አለመዳበር ጋር የተያያዘ ነው። ገንዘብ መሰብሰብና የውጭ ርዳታ የተወሰኑ ሰዎችን ሊጠቅም ቢችሉም የአንድን አገር መሰረታዊ ችግር ሊፈቱ አይችልም። ስለሆነም በተለይም የአገራችንን የተወሳሰበ ችግርና እንደዚህ ዐይነት ቫይረስም ሲከሰት ለመቋቋም ወይም ቶሎ ብሎ ለማስወገድ ከዚህ ዐይነት ሁኔታ ባሻገር ማሰብ ያስፈልጋል። አስተሳሰባችንን መቀየር አለብን። የመንግስትም ዋናው ተግባር የጀርመኑ ሁለት ፈላስፋዎች ሄገልና ሁምቦልድት እንደሚያስተምሩን የተሟላ ሰላምን በማስፈንና የተሟላ ነፃንትን በማክበር ላይ ያተኮረ መሆን አለበት። ከሁለት ሺህ ዐመት ተኩል በፊት የነበረውና የፍልስፍና አባት በመባል የሚታወቀው ፕላቶ በተለይም የፍትሃዊነትን ጉዳይ አጥብቆ ያነሳል። በዚህ መሰረት አንድ መንግስት ምን እንደሚመስልና ዋና ተግባሩም ምን እንደሆነ ትምህርታዊ በሆነ መልስ ያስቀምጣል። ስለሆነም ፍትሃዊነት በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጽ ሲሆን፣ ፍትሃዊነት በሌለበት አገር አንድ ህዝብ ተረጋግቶ ሊኖር አይችልም። አንድ ህዝብ ሰላምና ነፃነት ሲኖረው ብቻ ነው ሊያስብና ሊፈጥር የሚችለው። ከአንዳንድ የፈጠራ ማዕከሎች ባሻገር የህዝብ ነፃነት ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በትናንሽ ፈጠራዎች አማካይነት የአንድ ህዝብ መሰረታዊ ችግር ሊቀረፍ በፍጹም አይችልም። መሰረታዊው ጉዳይ የጠቅላላውን ህዝብ የማሰብ ኃይል ማዳበርና ራሱን እንዲችል ማድረግ ነው። እራሱን የሚያውቅ ሰው ደግሞ በምንም ዐይንተ ለጦርነት ወይም ለጠብ አይዘጋጅም። አስተሳሰቡ በሙሉ በፈጠራና በስራ ላይ ስለሚያተኮር ቅድሚያ የሚሰጠው ለእነዚህ ነገሮች ብቻ ነው።

በዚህ መሰረት አገዛዙ ዲሞክራሲያዊና ዘመናዊ ከመሆን ባሻገር የኢኮኖሚ ፖሊሲው መሰረታዊ በሆነ መንገድ መቀየር አለበት። ሰፊውን ህዝብ በአንድነት እንዲንቀሳቀስና አዲሲቱን ኢትዮጵያ እንዲገነባ የሚያስችለው መሆን አለበት። ይህም ማለት የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አሽቀንጥሮ መጣልና ኢትዮጵያ ነፃ አገር እንደሆነች ማወጅና መቀበልም ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ገበሬና ወጣት ሴቶች ለውጭ ገበያ በሚቀርብ ምርትና የአበባ ተከላ ላይ መሰማራት የለባቸውም። የአንድ አገር መንግስትና ህዝብ ዋናው ኃላፊነትና ተጠያቂነት በመጀመሪያ ደረጃ የራሱን ህዝብ መመገብና እንደዚህ ዐይነት ችግሮች ሲከሰቱ ለመቋቋም የሚያስችል ድርጅታዊ አዘገጃጀትን በየቦታው ማስፈን ነው። አንድ አገር በቂ ምርት ስታመርትና ሲተርፋት ብቻ ነው ወደ ውጭ መላክ የምትችለው። ስለሆነም የኢትዮጵያን ገበሬና ወጣት ሴቶች ወደ ባርነት የሚቀይር የኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ የኢንዱስትሪና የአበባ ተከላ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መቅረት አለበት።

ስለሆነም፣ 1ኛ) ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ላይ መሰማራት። 2ኛ) የህክምና መሳሪዎችን ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካና የምርምር ጣቢያዎች ማቋቋም። 3ኛ) የአገር ባህል መድሃኒቶችን ማጥኚያ ተቋማት በየቦታው ማቋቋምና በሳይንሳዊ ዘዴ እንዲጠኑ ማድረግ። 4ኛ) የሙያ ማስልጠኛ ጣቢያዎችን ማቋቋምና ወጣቱን ቴክኖሎጂዎችን እንዲማር ማድረግ። 5ኛ) የእርሻ መስኩን በአዲስ መልክ ማደራጀትና በቂና ልዩ ልዩ ምርቶች እንዲመረቱ ማድረግ። የእርሻ ምርት ምርታማነትን የሚያሳድጉ የእርሻ ምርት መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ ማምረትና ለገበሬው ማቅረብ። የእርሻው መስክ የግዴታ በትላልቅ ማሳዎች ላይ ብቻ የሚመካ ሳይሆን ልዩ ልዩ መልኮች የሚይዝ መሆን አለበት። በተለይም የገጠሩ ህዝብ እራሱን ለመመገብ የሚያስችለው በቂ መሬት እንዲኖረው ያስፈልጋል። 6ኛ) በየቦታው የተለያዩና ለችግር ጊዜ የሚሆኑ ሰብሎችን ለማጠራቀም የሚያመቹ ጎተራዎች በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ መስራት። ከዚህም ባሻገር ሌሎች እንደዘይት የመሳሰሉትን በአገር ውስጥ ማምረትና የተወሰነውንም ለችግር ጊዜ ማከማቸት። መንግስትም ሆነ ሌሎች የመንግስት ተቋማት ዋና ተግባራቸው በእንደዚህ ዐይነት መስኮች ላይ መረባረብ መሆን አለበት። ይህ አስተሳሰብ በጭንቅላታችን ውስጥ ሲቀረጽ ብቻ ነው በየጊዜው የሚከሰተውን እንደዚህ ዐይነት ችግር መቋቋም የሚቻለው። በተረፈ ግን ኮረና ቫይረስ እየተባለ ስለተወራና ስለሚራገብ በፍጹም መደናገጥ የለብንም። ጭንቀትና ፍርሃት በራሳቸው የሰውን በሽታ የመከላከል ኃይል ያዳክማሉና። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de