[gtranslate]

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር አለመተዋወቅ፣ የንቃተህሊና

    አለመኖር ወይም አለመዳበር፣ ጥያቄ ለመጠየቅ ያለመቻል ችግር ነው! ለአቶ ኤፍሬም   

  ማዴቦ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው? ብሎ ለጠየቀውናመልስም ለመስጠት ለመኮረውየተሰጠ ትችታዊና ሳይንሳዊ ሀተታ መልስ!! ቁጥር     

      Sometime people don`t want to hear the truth because they don`t want their illusion      

      destroyed. (Friedrich Nietzsche)

                                                                                                                                                                                                                      ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                                                                                                                                                            መጋቢት 17 2016(March 26,  2024)

 

መግቢያ

ኤፍሬም ማዴቦ “የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው? ብሎ ላቀረበው ጥያቄና መልስም ለመስጠት ለሞከረው፣ የሱን ጽሁፍ ተመርኩዤ ደረጃ በደረጃ ሰፋ ያለ ሂሳዊ ሀተታ ሰጥቼበታለሁ። ኤፍሬም ማዴቦም ሆነ አንዳንድ ጽሁፌን ያነበቡ ግለሰቦች የጽሁፌን መሰረተ-ሃሳብና የተመረኮዝኩበትን ሳይንሳዊ መሰረት ሳይረዱ ከጽሁፌ ጋር የማይጣጣም ወይም ጽሁፉን የማይመለከት ትችት ለማቅረብ ሞክረዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ከዓለም ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ሳይንሳዊ ሀተታዎችን በእንግሊዘኛ፣ በጀርመንኛም ሆነ በአማርኛ ቋንቋዎች በመጻፍ ለንባብ አቅርቤአለሁ። እነዚህም ጽሁፎች ደረጃ በደረጃ በድረ-ገጼ ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ። የተለያዩ ጽሁፎቼን ያነበበ ሰው ሊገነዘበው የሚችለው  ነገር አንዳችም ቦታ ላይ  ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከሰዎች ድርጊቶች፣ በተለይም የፖለቲካ ተዋናይ ነን ከሚሉትና፣ በተለይም ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ ረቅቀው ተግባራዊ ከሁኑ ነገሮችና አሉታዊ ውጤታቸው ውጭ የጻፍኩበት ጊዜ የለም። ጽሁፎቼ ከኢትዮጵያ ውጭ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም በመነበብ የድጋፍ መልዕክቶችና ያልገባቸው ነገሮች ካሉ በጥያቄ መልክም ደርሰውኛል። ኤፍሬም ማዴቦ ያቀረበውን ”የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ምንድነው?” የሚለውን ጽሁፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ያነበቡ ሰዎች ከጽሁፉ ብዙ ቁም ነገሮችን እንደተማሩ በኋትስ አፕ መልዕክት አስተላልፈውልኛል። እስካሁን እንድተከታተልኩት ከሆነ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አንዳንድ የማቀርባቸውን ክሪቲካል የሆኑ ጽሁፎቼን አስመልክቶ በሚገባ የማንበብና የመረዳት ችግር ያለባቸው ይመስለኛል። በአንዳንዶች ዘንድ  የሚታየው ይህ ዐይነቱ ችግር ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ዕውቀት በተስፋፋበትና፣ የተለያዩ የሳይንስና የፍልስፍና መጽሀፎች እንደልብ በሚገኝባቸው በአሁኑ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። መጽሀፍ ለመግዛት ቢከብድም እንኳ ካለምንም ወጭ ከመጻህፍት ቤቶች መጻፎችን በመዋስ በጣም ጠቃሚና ለጭንቅላት ገንቢ የሆኑ ዕውቀቶችን መቅሰም ይቻላል። በአሁኑ በኢንተርኔት ዓለምም አንዳንድ መጽሀፎችን ገንዘብ ሳይከፍሉ ማውረድና ማንበብ ይቻላል። ባጭሩ አንድ ሰው ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር የሚተዋወቅ ከሆነ በቀላሉ ግራ ሊጋባ አይችልም። እንዲያም ሲል ሳይንስ እያልክ ግራ አታጋባን ብሎ ሊጽፍ አይችልም። በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ጽሁፍ ትችታዊ በሆነ መልክ መገምገምና ተገቢው ሂስ መቅረብ አለበት። ተተቸሁ ብሎ ቡራ ከረዩ የሚል ሰው ከሌሎችም ለመማር የማይፈልግ ሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር አውቃለሁ የሚል ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ነገር በሂደት ላይ ያለ ነው። በየጊዜውም አዳዲስ ግኙቶችና ዕውቀቶች ይፈልቃሉ። በአንድ ዘመን ተቀባይነት ያላቸው ተሽረው በአዲስ ዕውቀቶች ይተካሉ። ይሁንና ግን ዘመን የማይሽራቸው ዘለዓለማዊ ዕውቀቶች አሉ። እነዚህም በሶክራተስ፣ በፕላቶንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ በግሪክ ፈላስፎች የተፈጠሩ ፍልስፍናዎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስ ዕውቀቶች ናቸው። እነዚህ ዕውቀቶች ደግሞ የኋላ ኋላ ላይ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአንዳንድ የአውሮፓ ፈላስፋዎች በመዳበርና ጥልቀትን በማግኘት ለተፈጥሮ ሳይንስ መሰረት ሊጥሉ ችለዋል። በአጭሩ ዘመን የማይሽራቸው ለሰው ልጅ የማቴሪያልም ሆነ የመንፈስ ዕድገት በጣም ጠቃሚ የሆኑ  ዕውቀቶች አሉ ማለት ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከተው ሰው ኤፍሬም ማዴቦ የጽሁፉን ይዘት በሚገባ ሳይረዳ  በቅድሚያ  ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መታገል ያስፈልጋል ብዬ እንደጻፍኩ አድርጎ  በማስመሰል የጽሁፉን አቀራረብ፣ የቲዎሪ መሰረትና የሀተታ ዘዴውን ሳይረዳ  የተሳሳተ ግምገማና ትችት ለመስጠት ሞክሯል። አንድነት ሰመረ የሚባል ግለሰብም እንደዚሁ የጽሁፌንና የአሰራር ስልትና የአተናተን ዘዴዬንና ሳይንሳዊ መሰረቱን ሳይረዳ ልክ ኤፍሬም ማዴቦ የጻፈውን በማስተጋባት ለመተቸት ሞክሯል። አልፎም በመሄድ “የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ስለማትረዳና የግራ አመለካከት ስላለህ ነው እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ የጻፍከው” በማለት ተራ ውንጀላ መሰል ነገር ለመሰንዘር ሞክሯል። ይሁንና ግን ራሱ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና ታሪካዊ ሂደቱን በምን መልክ እንደሚረዳ ለማስረዳት አልሞከረም። ይህ ብቻ ሳይሆን “የግራ አስተሳሰብ ስላለህ ነው እንደዚህ ብለህ የምትጽፈው ሲል” የግራ አስተሳሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ አልሞከረም። ይሁንና አንድነት ሰመረ ጽሁፌን በደንብ አንብቦ ከሆነ በአብዮቱ ወቅት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የህብረተሰብ አወቃቀር፣ እንዲሁም በጊዜው  ተፍ ተፍ በማለት አብዮቱን እናራምዳለን ወይም ለውጥ መምጣት አለበት ብለው ይታገሉ የነበሩ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ሁኔታውን በቲዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ ስላላጠኑ ብዙ ስህተቶች ሊሰሩ እንደቻሉ ለማብራራት ሞክሬአለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን የራስን ኢጎ በማስቀደም የተወሰዱ አመጻዊ እርምጃዎች በማንኛውም የማርክሲስት መጽሀፎች ውስጥ እንዳልተጻፉና፣ ይህም አመጻዊ ድርጊት ሊፈጸም የቻለው ከጭንቅላት ብስለት ጉድለትና የፖለቲካን ትርጉም ለመረዳት ካለመቻል የተነሳ እንደሆነ ለማተት ሞክሬአለሁ። ወደ መሬት ለአራሹና የቤቶችን ወረሳ ጋ ስንመጣ በሚገባ ሳይጠኑ ተግባራዊ እንዲሆኑ በመደረጋቸው በተለይም ጥሮ ግሮ ሀብት ያፈራውን ዝም ብሎ ፊዩዳል እያሉ በመወንጀል ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ሊፈጠር እንደቻለ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። እንደነዚህ ዐይነት ስህተቶችም ሊሰሩ የቻሉት የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎችና ደርግም ራሱ ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር ለመተዋወቅ ባለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን በንፅፅር ጥናት(Comparative Studies) በቻይናም ሆነ በሶቭየት ህብረት በአብዮት ስም በጅምላ ተግባራዊ እንዲሆኑ የተደረጉ ዕርምጃዎች በሙሉ ምን ዐይነት ጉዳት  እንዳስከተሉ ጠጋ ብሎ ለማጥናት ባለመቻሉ እነዚህን የመሳሰሉ ስህተቶች ሊሰሩ እንደቻሉ ግልጽ ነው። ሌላው አብዮተኛ ነን በሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የሚሰራው ትልቁ ወንጀል የታሪክን ሂደትና ውጣ ውረድነትን፣ በተለይም ደግሞ የንቃተ-ህሊናን ጉዳይ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የሚስተጋቡ መፈክሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ጥሩ እሴቶችንና ባህሎችን እንደሚያናጉና ህብረተሰብአዊ  መመሰቃቀልን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አለመረዳት ነው። ከዚህ ሁሉ ውስጥ አደገኛውና ለምሁራዊ እንቅስቃሴም እንቅፋት የሚሆነው በአገራችን ምድር የተሰሩትን ስህተቶችና ወንጀሎች በሙሉ በሶሻሊዝም ወይም በግራ አስተሳሰብ ላይ ማላከኩ ነው። በህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ወርቃማ መንገድ የለም። የሰው የማሰብ ኃይል እስኪዳብርና ረጋ እስኪል ድረስ ብዙ ዓመታትን ስለሚፈጅ እንደነዚህ ዐይነት ስህተቶች መሰራታቸው የታሪክ ግዴታ ነው።

ለምሳሌ የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመለትና በሶቭየት ህብረትም ሆነ በቻይና ውስጥ በአብዮቱ ዘመን ከተሰሩት ስህተቶች ወይም ወንጀሎች ጋር ስናወዳድረው በካፒታሊዝም የዕድገት የታሪክ ሂደት ውስጥ የተሰሩት ወንጀሎች በብዙ እጅ እንደሚበልጡ መታወቅ አለበት። በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ገበሬው በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝና እንደ ግል ሀብትም ይቆጠር ነበር። ከባላባቱ ፈቃድ የሚያርስበትን መሬትና የሚኖርበትን ጓሮ ጥሎ የመሄድ መብት አልነበረውም። ገበሬው ለማግባት ከፈለገ ባላባቱን ፈቃድ መጠየቅ ነበረበት። ይህንን ዐይነቱን ጭቆናዊ ድርጊት በመቃውም በፊዩዳሉና በገበሬው መሀከል ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል። በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የሰፈነውን ጭቆናዊ አገዛዝና ጭፍን የሆነውን የካቶሊክ ርዕዮተ-ዓለም የተቃወሙና ትክክለኛውን ሳይንሳዊ መንገድ ለማሳየት የሞከሩና ያረጋገጡም ከነነፍሳቸው እንዳሉ ተቃጥለዋል። ብዙ ምሁራንም አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ለመደርግ በቅተዋል። ካፒታሊዝምም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ የባርያ ንግድና ቅኝ-ግዛት ተስፋፍተዋል። በእነዚህ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ ነው ካፒታሊዝም ከፍተኛ የሀብት ክምችት ማዳበር የቻለው። አሜሪካ የተቆረቆረቺው 17 ሚሊዮን የሚያህሉ ኢንዲያኖችን በማረድና ታሪካቸውንና ስልጣኔያቸውን በማውደም ነው። የኋላም ኋላም የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች ሰለጠንኩ በሚለው በካፒታሊስቱ ዓለም የተቀሰቀሱና ለብዙ ሚሊዮኖች ሰዎች ህይወት መቀሰፍ ምክንያት የሆኑ ናቸው። ባጭሩ ለማለት የምፈልገው የግራ አመለካከትን ወይም የሶሻሊስት አስተሳሰብን የሚቃወም ወይም ይህን አስተሳሰብ ያራምዳሉ የሚላቸውን የሚወነጅል ሰው ወይም ቡድን በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ሁሉ ማወቅም አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን መጻፍና ማብራራትም አለበት።  በሌላ ወገን ግን አንድነት ሰመረ ያልተረዳው ነገር እሱ እኔን “የግራ አመለካከት ያለህ ነው” ብሎ ሲወነጅለኝ ራሱ የቀኝ ወይም ፋሺሽታዊ አመለካከት ያለው ለመሆኑ ያለመረዳቱ ነው። በመሰረቱ በሳይንስ ዓለም ውስጥ የግራና የቀኝ አስተሳሰብ የሚል አቀራረብ የለም። ሳይንስ ሳይንስ ስለሆነ ማንኛውም የተፈጥሮንም ሆነ የህብረተሰብን አወቃቀር በሚመለከት አንድ ሰው ጽሁፎችን መጻፍ ያለበት ሳይንሳዊ መሰረትን ምርኩዝ በማድረግ ብቻ ነው። ይህም ማለት የህብረተሰብን አወቃቀር ሁለንተናዊ በሆነ መልክ ከቲዎሪም ሆነ ከኢምፔሪካል አንፃር በመመርመር ብቻ ነው።

ይሁንና በህብረተሰብ የግንባታ ታሪክ ውስጥ በአገሮች ውስጥ የፖለቲካ መዛባት፣ እንዲያም ሲል የጭቆናና የሀብት ክፍፍልና የድህነት ጥያቄዎች፣ ማለትም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች አፍጠው አግጠው የነበሩ ጉዳዮች ስለሆኑና፣ በተለይም ስልጣንን የጨበጡና ተጠቃሚ ኃይሎች ሀብትን በተስተካከለ መልክ ለማከፋል ስለማይፈልጉና የማህበራዊ ችግሮችም እየጎሉ ስለመጡ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ወደ ህብረተሰብአዊ ግጭት እንዳይሸጋገር የግዴታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍትሃዊነት መስፈን እንዳለበት አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን በተለይም ተጨቆነ፣ ወይም ተበደለ ከሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ጎን በመቆም ለፍትሃዊነት ታግለዋል። አንዳንዶችም ቀደም ብለው በመሄድና ሳይንሳዊ ሀተታ በመሰጠት ለመሰረታዊ ለውጥ ታግለዋል። እነዚህ ዐይነቱ የተገለጸላቸው ምሁራን ለመሰረታዊ ለውጥ ሲታገሉ በ19ኛው ክፍለ-ዘመንና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ  የነበረውን የድህነት መስፋፋት፣ የከተማዎች መቆሸሽና፣ በተለይም በየፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን የስራ ሁኔታና በሰውነታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በሚገባ ከተመለከቱና፣ የፋብሪካም ስራ በዚህ መልክ መዋቀር የለብትም ብለው ሰፋ ያለ ሀተታ መስጠት ከጀመሩ በኋላ ነው። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት ሲካሄድ ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ በከፍተኝ ደረጃ የሚጎዱ ነገሮች ስለተከሰቱና ህብረተሰቡም በከፍተኛ ደረጃ መመሰቃቀል ስለጀመረ የግራ ወይም የማርክሲዝም አስተሳሰብ ከመስፋፋቱ በፊት የሰብአዊነት ባህርይ ያላቸውና ጠለቅ ብለው የሚያስቡ ምሁራን በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ በዚህ መልክ መካሄድ የለበትም በማለት ይታገሉ ነበር። ይህም የሚያመለክተው እንደኛ አገር ሳይሆን በአውሮፓ የምሁራን እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ የነገሮችን ሂደት ትችታዊ በሆነ መልክ የመመልከትና ሀተታ የመስጠት ልምድ ስላለ  እንደኛ አገር ዝም ብሎ የሚታለፍ ነገር የለም።  አብዛኛዎችም ሀተታዎች በአቦሰጡኝ ሳይሆን የሚጻፉት በስልትና ሳይንሳዊ መሰረተ-ሃሳብን በማስደገፍ ብቻ ነው። በጭፍን መጓዝ የተለመደ ነገር አይደለም ማለት ነው። በሌላ ወገን ያለው ሁኔታ መለወጥ ወይም መሻሻል የለበትም ብለው የሚታገሉና ሳይሰሩና ሳይንቀሳቀሱ ሌላው በሰራው ተንደላቀው ለመኖር የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ። እነዚህም ቀኝ የሚባል ስም ተስጥቶአቸዋል። አንዳንዶችም ከዚህ ገፍተው በመሄድ ወዝአደሩንና መሪዎችን፣ ወይም የእሱን ጥቅም ያራምዳሉ የሚባሉ ምሁራንን እንደዋና ጠላት በማየት ያሳድዱና ይገድሉ እንደነበረ ይታወቃል። እነዚህ ኃይሎች የኋላ ኋላ አደገኛ አዝማሚያ በመውሰድ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር በመዳበል ለፋሺዝም እንቅስቃሴ መነሳት እንደዋና ምክንያት ለመሆን በቅተዋል።

ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ የህዝብ ኑሮ መሻሻል አለበት፣ የኢኮኖሚው እንስቃሴና ዕድገት ሰፋና በጠነከረ መሰረት ላይ መገንባት አለበት ብሎ መታገል የግራ አመለካከት ተብሎ ሊወነጀል የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ለውጥ ወይም መሻሻል አያስፈልገንም የሚል ሰው ካለ የግዴታ እዚህ አገር የቀኝ ወይም የፋሺሽት ኃይሎች ከብዙ አስርት ዓመታት ጀምሮ እንደሚታገሉት የራስን አቋም ግልጽ በማድረግ መታገል የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ካለበለዚያ የሰውን አስተሳሰብ የግራ አስተሳሰብ እያሉ ማስፈራራት ኃይልን መበታተንና ብዙ ነገሮች ተድበስብሰው እንዲቀሩ ማድረግ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በምንም ዐይነት ለውጥ አያስፈልግም ማለት ነው። ስለሆነም የእኔ አቀራረብ የአገራችንን ሁኔታ በሚገባ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መልክ መነበብና መጠናት ስላልተቻለና ልምድም ስለሌለን ነው እንደዚህ ዐይነቱ መወናበድና ዕልቂት ለመድረስ የቻለው ስል  ትግላችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ያትኩር ማለቴ ሳይሆን በጭንቅላት ዙሪያና መንፈስን በማጎልበስ መሰራት የነበረባቸው ነገሮች ስላልተሰሩ አብዮተኛ ነኝ ይል የነበረው ታጋይና መሪዎቻቸው ከመደማመጥ ይልቅ እንደ ጠላት በመተያየት ወደ መሳሪያ ትግል አመሩ ለማለት ፈልጌ ነው። የመሳሪያን ትግል የሚያስቀድምና ወደ አመጽም የሚያደላ ግለሰብም ሆነ ቡድን ጭንቅላቱ በሚገባ ያልተኮተኮተ ስለሆነ በመሰረቱ ሰፋ ያለና ለጭንቅላት መዳበር፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚያመቸውን በሁሉም መልክ የሚገለጸውን ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲዳፈን ያደርጋል። በተግባርም ያየነው ይህንን ሀቅ ነው። በትግራይ ክልልና በኤርትራ ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች ይህንን ነው የሚያረጋግጡት። በአገራችንም ምድር የሚታየው ሁኔታ ከምሁራዊ እንቅስቃሴ የራቀና በአመጽ ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ነው። ፖለቲካን ወደ ማወናበድ፣ ወደ ተራ ተንኮልና ወደ ሽብርተኝነት የለወጠ አገዛዝ ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የፖለቲካውን መድረክ በመቆጣጠርና የመጨቆኛ መሳሪያውን ተገን በማድረግ አገራችንን በሁሉም መልክ በማዘበራረቅ ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ፈሩን እንዲስት አድርጎታል።

ኤፍሬም ማዴቦ የኢኮኖሚ ችግር አለ፣ ደርግም የተከተለው የማይገባውን የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ሲል፣ ይህ ትክክል አለመሆኑና ደርግ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን የአገራችንን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ በማሳየት፣ ከአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተሳሳተ መሰረት ላይ ለመመርኮዝ በመቻሉ ይህ ሁኔታ ለኢኮኖሚ ዝቅጠትና ለማህበራዊ ሁኔታ መዳከም እንደዳረገን ለማሳየት ነው የሞከርኩት። አንድነት አስመረ ጽሁፌን መስመር በመስመር በሚገባ ቢያነብ ኖሮና ቀድም ብዬ ካወጣኋቸው አያሌ የኢኮኖሚ ጽሁፎቼ ጋር ቢያወዳድር ኖሮ ተራና ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ ውንጀላ ውስጥ ባልገባ ነበር። የኤፍሬም ማዴቦንም ጽሁፍ በሚገባ ካነበብኩ በኋላ ነው መሰረታዊ ትችት ለመስጥት የሞከርኩት እንጂ ሙሉ የምትባል ሌላዋ ተቺ እንደምትለው ግራ ለማጋባት የጻፍኩት ነገር አይደለም። ሁልግዜ ግራ የሚጋባ ሰው መሰረታዊ ዕውቀት የሌለውና መጽሀፎችንም የማንበብ ልምድ የሌለው  ሰው ብቻ ነው። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ኤፍሬም ማዴቦ ባነሳው ጥያቄና በእኔ ግምት ግልጽ ያላደረጓቸው ነገሮች አሉ በምላቸው ነገሮች ላይ አንዳንድ ማብራሪያዎችን እንደገና ለመስጠት እሞክራለሁ። እንደገና ስል ቀደም ብዬ ባወጣኋቸው አንዳንድ ጽሁፎቼ ላይ ብዙ ነገሮችን ለማብራራት የሞከርኩ ስለነበር በዚኸኛው ጽሁፌ ላይ እንደገና ለመመለስ ስላልፈለጉ ዝምብዬ ስላለፍኩ አንባብያን ግራ ተጋብተው ይሆናል በሚል አስተባብ ብቻ  ነው።

 

እረ ለመሆኑ ሳይንሳዊ ዕውቀት ሲባል ምን ማለት ነው?

“የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋናው ችግር ከሳንይሳዊ ዕውቀት ጋር አለመተዋወቅ ነው” ስል በመጀመሪያ ደረጃ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መታገል ማለቴ ሳይሆን፣ ተፈጥሮንም ሆነ የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀር ጠጋ ብሎ በማየት(Observe) ከላይ ከሚታዩት ነገሮች በማለፍ ተፈጥሮንንም ሆነ ህብረተሰብን ምን ምን ነገሮች እንደሚያያዛቸውና፣ እንዴትስ አንደኛው ነገር በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ለመረዳት መሞከር ማለት ነው። የተፈጥሮን ነገር ትተን ወደ ህብረተሰብ ጋ ስንመጣ፣ ከመንግስት አወቃቀር አንስቶ ሰለፖለቲካ አወቃቀርና፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ያሉትን ነገሮች ደረጃ በደረጃ ማጥናት ያስፈልጋል። የእነዚህ ነገሮች ደግሞ በስርዓትና በጥናት ወይም ደግሞ ያለስርዓትና ካለጥናት መዋቀር በጠቅላላው ህብረተሰብ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንድንገነዘበው ይረዳናል። ለዚህ ደግሞ ሳይቻኮሉ ጊዜ በመውሰድ ጥናትና ምርምር በማድረግ ብቻ ነው መገንዘብ የሚቻለው። በጥናትና በምርምር መልክ የሚታገዝ ግምገማ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለዕድገት፣ ለስልጣኔ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን እንድናውቅና ቀስ በቀስም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ እንዲወሰዱ ግፊት ለማድረግ ያስችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን በጥናትና በምርምር ላይ የሚደገፍ ህብረተሰብአዊ ሀተታ ለተከታታዩ ትውልድም እንደመነሻ በመውሰድ በዚያው እንዲቀጥል ይገፋበታል፤ የማሻሽልና የማስፋፋት ዕድልም ያገኛል።

የአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ስልጣንን በተቆናጠጡ ወይም በመንግስት ብቻ የሚሳበብ አይደለም። አንድን ህብረተሰብ የሚያያዙ ልዩ ልዩ ባህሎችና እሴቶች፣ እንዲሁም የፈጠራ ስራዎች በሙሉ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በግለሰቦች ወይም በቡድን የሚፈጠሩና የሚተገበሩ ናቸው። የሃይማኖትን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ለምሳሌ የእርሻ ስራንና በኢትዮጵያ ምድር የተገኙትን ሰብሎችና መራባት ስንመለከት ገበሬው በማየት፣ በሙከራና በልምድ ያስፋፏቸው ናቸው። ለምሳሌ ጤፍ በየትኛው ክፍለ-ዘመን እንደተገኘና ገበሬውም ለምን ጤፍን እንደ እህል በመቁጠር በመዝራትና ለምግብ እንዲውል ማድረጉ የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የአስተራረስ ባህልና እንደጤፍ የመሳሰሉትን ለምግብ እንዲሆኑ ማድረግ ራሱን የቻለ የፈጠራ ችሎታ ብቻ ሳይሆን፣ አንደኛው የዕድገት መገለጫና ህብርተሰብአችንንም ለማያያዝ የቻለ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዚህ ረገድ ገበሬው በረቀቀ መልክ በማሰብና ልዩ ልዩ ሰብሎችንና ለዘይት የሚሆኑ እንደተልባና ሰሊጥ፣ እንዲሁም ኑግ የመሳሰሉትን በመዝራትና በማስተዋወቅ በአገራችን ምድር የምግብ አብዮት እንዲካሄድ ለማድረግ በቅቷል። እናቶቻችንም ይህንን ዕድል በመጠቀም እንጀራና ዳቦ በመጋገር ለአገራችን የባህል ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማበርከት ችለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ጠላ፣ ጠጅና ካቲካላ የመሳሰሉትን እዚያው አገር ውስጥ በመፍጠርና በመጥመቅ የባህል መጠጦች እንዲሆኑ ለማድረግ በቅተዋል። የእነዚህን መጠጦች አጠማመቅ ስንመለከት ደግሞ ሳይንሳዊ ናቸው። ለምሳሌ የካቲካላን አጠማመቅ ስንመለከት ለካቲካላ የሚሆን የእህል ዐይነት ዳጉሳ ብቻ ነው። ይህ እህል በመጀመሪያ ደረጃ በውሃ እንዲበቅል ከተደረገ በኋላ ከጌሾ ጋር በመዋሃድ በመቆምጠጥ በስሎ ድፍድፉ በጋን ውስጥ ተቀምጦ በትንሽ እሳት እንዲበስል ይደረጋል። የተወሰነ የቴምፕሬቸር መጠን ላይ ከደረሰ በኋላ እንፋሎቱ በቀርቀሃ ጠብ ጠብ  በማለት ካቲካላ ይወጣዋል። የካቲካላ አጠማመቅም ሂደት ኬሚካላዊና ፊዚክስ ነው። መኮምጠጡ የኬሚካል ሂደት ሲሆን፣ ሲቀቀልና ወደ እንፋሎት ተለውጦ ካቲካላ ሲሆን ደግሞ ፊዚክስ ነው። ባጭሩ እናቶቻችን በኢንቲዩሽን  ደረጃ ሳይንቲስቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የካቲካላና የጠላ አጠማመቅ በማዕከለኛው ዘመን በምዕራብ አውሮፓ የተለመደና ቀስ በቀስም ወደ ኢንዱስትሪ ምርትነት የተለወጠ ነው። ጌሾም በአውሮፓ ምድር የተስፋፋና ለቢራ ጠመቃና ለልዩ ልዩ የአልክሆል መጠጦች መጥመቂያ የሚያገለግል ነው። ይህንን ሁኔታ ስንመለከት በጥንት ዘመን አንደኛው አገር ከሌላው ሳይኮርጅ በማየት፣ በሙክራና በልምድ ብዙ ነገሮችን እንዳገኘና እንደፈጠረ ለመገንዘብ እንችላለን።

ወደ አባባሌ ስመጣ ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር ስላልተዋወቅ ነው እንደዚህ ዐይነቱ ወንጀል ለመሰራት የተቻለው ስል ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ማለት የአንድን ህብረተሰብ ምንነት፣ የተጓዘበትንና በሂደት ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈጠሩ፣ ይሁንና ደግሞ ለህዝብ ጠቀሚታ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ለመጠናት ባለመቻላቸውና በቁንጽል አስተሳሰብ ላይ ብቻ መረባረብ ስለተጀመረ የማያስፈልግ ግብግብ ውስጥ ለመግባት ቻልን ማለቴ ነው። እንደዚህ ስል ግን የመሬት ላራሹ የመሳሰሉት ነገሮች በተጠናና ፊዩዳል የሚባለውንም የህብረተሰብ ክፍል በማይጎዳ መልክ መታወጅና መተግበር የለባቸውም ማለቴ አይደለም። በማንኛውም አገር፣ በተለይም ደግሞ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥም የጥገና ለውጦችና እንዲያም ሲል ገበሬውን ከቀየው ሳያፈናቅሉ የኢንዱስትሪ አብዮት የመሳሰሉትና በአጠቃላይ ሲታይ ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ዕድገት ለመምጣት ባልቻለ ነበር። በሌላ ወገን ግን የሚነሳው ጥያቄ ጥገናዊ ለውጥም ሆነ የኢንዱስትሪ አብዮትን ለማካሄድ የግዴታ ገበሬው ከመሬቱ መፈናቀል አለበት ወይ? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በጊዜው የነበረው አስተሳሰብ ፊዩዳላዊ ስለነበረና ፖለቲካ የሚባለው አስተሳሰብ ስር የሰደደ ስላልነበረና የኃይል አሰላለፉም ለከበርቴው መደብ የሚያደላ ስለነበር ገበሬው ዝም ብሎ ከማየት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረውም።  ይሁንና ግን በአጠቃላይ ሲታይ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ በተጠና መልክና በዕቅድ አንድን ህብረተሰብ የሚጠቅሙና እንደማህበረሰብም የሚያያዙት ነገሮች ቀሰ በቀስ ተግባራዊ መሆን አለባቸው። ካለጥገናዊ ለውጥ መሻሻልና ዕድገት በፍጹም ሊታዩና ሊመጡ አይችሉም።

በአጠቃላይ ሲታይ የህብረተሰብአዊ ለውጥን ሂደት ስንመለከት ስልጣኔ ሊመጣ የቻለው ጥቂት ምሁራን የማሰብ ኃይልን ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ነው። ምክንያቱም የማሰብ ኃይሉን ለመጠቀም የማይችል ሰው ወይም የህብረተሰብ አካል ኃይልን ስለሚያስቀድም የግዴታ በቀላሉ እልባት ሊያገኝ የማይችል ህብረተሰብአዊ ውዝግብ ውስጥ ይገባል። ህብረተሰብአዊ  ውዝግብ ባለበታገር ውስጥ ደግሞ አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል በታጠቀው መሳሪያ በመተማመን ረብሻ የሚፈጥር ከሆነ የሰው ልጅ የመፍጠር ኃይል እንዲታፈን ያደርጋል። የእያንዳንዱም ግለሰብ አስተሳስብ በማያስፈልጉና ለራስም ሆነ ለህብረተሰብ በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ እንዲጠመድ ያደርጋል። በግሪክ ምድር በጊዜው የነበረውን በተለይም በፈረጠሙ ኃይሎች ይደረግ የነበረውን የእርስ በርስ ሽኩቻ ምክንያቱን ለማወቅ የግሪክ ፈላስፋዎች መነሻ ያደረጉት የጭንቅላትን ሁኔታ በመመራመር ነበር። ፕሌቶ የሚባለው ታላቅ ፈላስፋ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በደንብ ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምደማ “የሰው ልጅ ችግር የማሰብ ችግር ነው”( Problem of Thought) በማለት በትክክል ያስቀምጣል። ፕሌቶ ይህንን ምርኩዝ በማድረግ በዕውነተኛ ዕውቀትና በተሳሳተ ዕውቀት መሀከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። በፕሌቶ ዕምነት ትክክለኛ ዕውቀት ከጭንቅላት ውስጥ በማሰብ ወይም በመመራመር ኃይል የሚገኝ ነው። ትክክለኛ ያለሆነ ዕውቀት ግን በምናያቸውና ይህንን ያህልም በጥልቀት ለማስበ በማንችልባቸው(Sense Preception) ነገሮች ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ የዚህ ዐይነት ዕውቀት በማሽተት፣ በማየት፣ በመነካካት ባጭሩ በአምስቱ የሴንስ ኦርጋኖች ላይ በመመርኮዝ የሚገኝ ዕውቀት ነው። ይህ ዐይነቱ ዕውቀት በነገሮች መሀከል መተሳሰብ እንዳለ፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችልና፣ በተለይም ደግሞ የታሪክን ሂደትና የሰውም ልጅ በሂደት ውስጥ ያካበታቸውን ነገሮች ከቁጥር ወይም ከግምት ውስጥ የማያስገባ ነው። ባጭሩ ይህ ዐይነቱ ዕውቀት በውጫዊው ዓለም ላይና በዛሬው ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ዕውቀት ሰለተፈጥሮም ሆነ ስለህብረተሰብ አገነባብ ዕውነተኛ ግንዛቤ ሊሰጠን አይችልም። በዚህ ዐይነት አስተሳስብ መንፈሱ የተቀረፀ ሰው ነገሮችን ከሁለመንታዊ አንፃር ጠጋ ብሎ የመመራመር ኃይል በፍጹም የለውም። ስለሆነም በቁንጽል አስተሳሰብ በመጠመድ ጠቅላላው ህብረተሰብ እንዲናጋ ያደርጋል። በተለይም በዛሬው ወቅት በአገራችንም ሆነ በተቀረው ዓለም የምንመለከተው መወናበድና በየአገሮች ውስጥ ውዝግብ መፈጠር ዋናው ምክንያት በተለይም የኤሊቱ አስተሳሰብ በዚህ ዐይነቱ ቁንጽል አስተሳሰብ ስለተጠመደ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በታሪክ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ አገር ውስጥ ጦርነት፣ ኢ-ፍትሃዊነትና በአጠቃላይ ሲታይ ማህበራዊ ውዝግቦች የሚፈጠሩት ሳይንሳዊ ዕውቀት ባልተስፋፋበትና፣ በተለይም ደግሞ መንግስት የሚባለው አካል ራሱን ከማደለብ ባሻገር ህብረተሰብን በስርዓትና ምርታማ እንዲሆን ለማደራጀት ብቃትነት ወይም አስፈላጊው ዕውቀት የሌለው ከሆነ ብቻ ነው። ስለዚህ ነው ከጥንት ግዜያት ጀምሮ ሰለመንግስት ፍትሃዊ በሆነ መልከ መዋቀር ጉዳይ፣ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ ሰዎች ደግሞ አይ ፈላስፋዎች መሆን እንዳለባቸው አሊያም ደግሞ በፈላስፋዎች የሚመከሩና ሁለ-ገብ ፖሊሲ በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው መሰበክ ወይም ማስተማር የተጀመረው። ይህ ዐይነቱ ያልተቋረጠ ትግልና ምሁራን ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣንን ለመያዝ ሳይሆን የበለጠ መመራመር ያስፈልጋል ብለው በማትኮር ለተለያዩ ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ ዕውቀቶችን በማፍለቅና ከአገሮቻቸው አልፈው ዓለም አቀፋዊ ማድረግ የጀመሩት። ስለዚህም ነው በግለሰቦች ጥረትና ምርምር የተነሳ ማቲማቲክስ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማለትም እንደ ፊዚክስ፣ ባይሎጂና ኬሚስትሪ የመሳሰሉት ዕውቀቶች በሙሉ በመፈጠር ተፈጥሮን የበለጠ በመቃኘትና በመመራመር እንዲሁም ምስጢሩንም በመረዳት በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን አውጥቶ ወደ መሳሪያነት በመለወጥ ልዩ ልዩ ነገሮችን መፍጠርና ማመረት የተቻለው። ቀደም ብለው በተለያዩ አገሮች የተፈጠሩት ዕውቀቶች፣ የከተማ አገነባቦች የኋላ ኋላ ለአውሮፓው ስልጣኔና ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት መጣል እንደቻሉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ከመንግስት አወቃቀር አንስቶ፣ እስከ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ስለከተማ ግንባታዎችና መንደሮች አወቃቀር ሁኔታዎችን ስንምረመር የምናገኘው ሀቅ አብዛኛው ነገሮች በአቦሰጡኝ  የተሰሩ እንጂ በከፍተኛ ምርምርና ጥናት እንዳልሆኑ መገንዘብ እንችላለን። ይህንን ለማወቅ ደግሞ የተወለድንባቸውንና ያደግንባቸውን መንደሮችና የገጠሩን ሁኔታ ወደ ኋላ መለስ ብለን ለማየትና ለመመራመር መቻል አለብን። ለምሳሌ በተወለድንበት መንደር ወይም ገጠር ውስጥ በስርዓት ወይም ጥበባዊ በሆነ መልክ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች አሉ ወይ? የትምህርትቤቶችስ አገነባብና ሁኔታ ምን ይመስላል? ቤተመጻህፍቶችስ አሉ ወይ? በተወለድንበትና ባደግንበት መንደር ውስጥ ከትምህርትቤት ውጭ ለመንፈሳችን መዳበር የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ተዘጋጅተዋል ወይ? እያልን ጥያቄ ለማቅረብ ብንሞክር አብዛኛዎች ነገሮች ካለማሰብ ወይም ከምርምርና ከጥናት ውጭ እንደተሰሩ በቀላሉ ለመገንዘብ እንችላለን። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የግዴታ በአስተሳሰባችንና በአዕምሮአችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ  ለማሳደር እንደቻለ ካለብዙ ጭንቀት መገንዘብ ይቻላል።

ይህንን ትተን ወደ ምንማረው ትምህርት ጋ ስንመጣ ትምህርቱ በዚያ መልክ ለምን እንደተዘጋጀና ለምንስ ዓላማ እንደተዋቀረ ሊነግረን የሚችል ሰው የለም። ይሁንና ግን ካለበቂ ጥናትና ካስፈላጊው ሁኔታዎች ውጭ መሰረተ-ትምህርትቤቶችም ሆነ የመለስተኛና የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ትምህርትቤቶች እዚህና እዚያ ተቋቁመዋል። ይህ ዐይነቱ ካለብዙ ምርምርና ጥናት እንዲሁም ጭንቅላትን በሁሉም አቅጣጫ እንዲያዳብር ሆኖ ያልተዘጋጀው የትምህርት አሰጣጥና የአስተማሪዎችም ሁኔታ የግዴታ ለጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት መሰረት ሊሆን ችሏል። በዚህ መልቅ የተዋቀረው ጭንቅላታችን የኋላ ኋላ በቁንጸል መልክ ተግባራዊ ከሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በመዳበል ሳንወድ በግድ አመጸኛ ሊያደርገን በቅቷል። እንዲያም ሲል ለመደማመጥ የማይችልና ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ ለማየትና ለማንበብ የማይችል ትውልድ በመፈጠሩ ሁሉም ባይሆን የተወሰነው ጥራዝ-ነጠቅ በመሆን አገራችንን ወደ ማይሆን አቅጣጫ ሊመራት ችሏል ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ የነገሮችን ሂደት፣ በጊዜው የነበረውን የመንግስት መኪና አወቃቀር፣ በአጠቃላይ ሲታይ ፖለቲካ ብለን የምንጠራው፣ ይሁንና ደግሞ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ የሰፈነበት፣ ወይም ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ ያለነበረበት ሁኔታና፣ ሁሉም ነገሮች በግብታዊ መልክ ይካሄዱ ስለነበር የኋላ ኋላ አመጸኛ ሊያደርገን በቅቷል ማለት ይቻላል። እነዚህ ነገሮች ደረጃ በደረጃ ሳይጠኑና፣ በተለይም ደግሞ የመንግስትን ምንነትና ሚና ሳይረዱ በአቦ ሰጡኝ የሚወሰዱ ፖሊሲ ነክ እርምጃዎች መንፈሱን ለመሰብሰብና በቅጡ ለማሰብ የማይችል የህብረተሰብ ኃይል እንዲፈጠር ለማድረግ በቅቷል። ይህ ሁኔታ የግዴታ ጥራዝ ነጠቅነትን ከማስፋፋት አልፎ፣ የነገሮችን አመጣጥና ሂደት በጥናት ላይ በመመርኮዝ ሀተታ ከመስጠት ይልቅ ወደ ተሳሳተ ትረካ ላይ ለመድረስ ተችሏል። ለዚህም ነው በጊዜው የመደብ ትግልና የብሄረሰብ ጥያቄ ወይም የጭቆና ጉዳዮች ሊነሱ የቻሉት። እነዚህ ነገሮች በመነሳታቸው፣ እንደፋሽን በመወሰዳቸውና ጭንቅላታችንን በመያዛቸው ነው ለአንድ አገርና ህብረተሰብ ጠቃሚ የሆኑት እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስ፣ የከተማ አገነባብ፣ የሶስዮሎጂና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የስነ-ልቦና ዕውቀቶች አትኩሮ ሊሰጣቸው ያልተቻለው። አሁንም ቢሆን በእነዚህ ዙሪያ ጥናት የሚያካሂድና ሀተታ በማቅረብ ታዳጊውን ትውልድ የሚያስተምር የለም። አብዛኛው የተረት ተረት በማውራት ጊዜውን እንዲያሳልፍና ህዝብን እንዲያደናግር ዕድል ለማግኘት ችሏል።

ከላይ እንዳልኩት እነፕሌቶ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለን ችግር ለማጥናት የሞከሩት ትክክለኛ ዕውቀት በሌለበትና የማሰብ ኅይል ባልዳበረበት፣ በተለይም ደግሞ የገዢው መደብ ፍልስፍናዊ ዕውቀት ከሌለው፣ ወይም በፈላስፋዎች የማይመከርና የማይመራ ከሆነ የግዴታ ኢ-ፍትሃዊነትና ያልተሰተካከለ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ነው። ይህም ማለት የገዢው መደብ የተሳሳተና ኢ-ፍትሃዊነት ያለው ፖለቲካ የሚከተለው ወይም አመጽን የሚያስቀድመው ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት ያልታነፀ ከሆነ ብቻ ነው። ስለሆነም የማህበራዊ ውዝግቦች ዋናው መነሻ በቁንጽል አስተሳሰብ በመመራት ኃይልን ማስቀደም ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጭንቅላት ወይም የማሰብ ኃይል ባልዳበረበት አገር ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮችና አንድን ህብረተሰብ ፈሩን እንዲለቅ የሚያደርጉት ነገሮች ታስቦበት(Intentionally) የሚካሄዱ ሳይሆን ካርቆ ማሰብ ጉድለት የሚተገበሩ ስለሚሆኑ ብቻ ነው።

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ በጊዜው የነበሩትን የብሄረሰብን ሁኔታና ሌሎች ኢ-ፍትሃዊ ነገሮችንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ድህነትን ፈልፋይ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መተግበር ጉዳይ ለመረዳት የተቻለው በቀላሉ ህብረተሰባችን በመደብ ስለተከፋፈልና የመድብ ትግል ስላለና የብሄረሰብ ጭቆና ስለሰፈነ ነው የሚል ነው። ይህ ዐይነቱ ግንዛቤ የአገራችንን አጠቃላይ ሁኔታ ከዕውቀት ማነስ ጋር ለማያያዝ ካለመሞከርና፣ በተለይም ደግሞ በቲዎሪ ደረጃ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና የሶስይሎጂ ምርምሮች ባልተስፋፉበት አገር ውስጥ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት ነው። በተለይም የብሄረሰብ ጥያቄ አነሳስ በሚገባ ሳይጠና የተነሳና ማለቂያ ወደሌለው ውዝግብ ውስጥ ወይም ደግሞ ከዚህም ከዚያም ለፈለቁ የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ መሬ ነኝ ለሚሉ፣ በመሰረቱ ዕውቀት ለሌላቸውና አመጽን ለሚያስቀድሙ መፈንጫ መድረክ የከፈተ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ነገሩን የበለጠ ለመረዳት በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚና የትምህርት ፖሊሲዎች በሙሉ አንድን ብሄረሰብ ብቻ ለመጥቀም ተግባራዊ የሆኑ አልነበሩም። ኢ-ሳይንሳዊ የሆነውና ለጥቅላላው ህዝብ ብሄራዊ ሀብት ለማዳበር የማይችለውና ለፈጠራና ለተከታታይ ምርምር መሰረት ሊሆን የማይችለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወይም አብዛኛው  ብሄረሰብ በድህነትና በኢ-ፍትሃዊነት የሚማቅበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ብዙ መማር አያስፈልግም። በቀላል ዕይታና ጥናት የነበረውን ሁኔታ መረዳት ይቻላል። ለማንኛውም ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ለማሰብ ባለመቻሉ ወይም ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር ልምምድ ስለሌለንና የነገሮችን አነሳስና ሂደት ጠጋ ብሎ መመልከት ስለማንፈልግ በተሳሳተ ትረካ ላይ ብቻ በመመርኮዝ ማለቂያ ወደሌለው ግብግብ ውስጥ ለመግባትና አገርን ለማፈራረስ በቅተናል። ባጭሩ የኤፍሬም ማዴቦ ጥያቄ አነሳስና መልስም ለመስጠት ያለመቻል በዚህ መልክ ነው ግልጽ መሆን ያለበት። ስለሆነም የአገራችንንም የተወሳሰቡ ´ችግሮች መፍታት የምንችለው በሳይንሳዊ ዕውቀት እንጂ እዚህና እዚህ ውርውር በማለትና ሰፊውን ህዝብም በማሳሳት አይደለም።

የንቃተ-ህሊና ያለመዳበር ጉዳይ የሚያስከትለው ችግር!

በፈላስፋዎች፣ ንቃተ-ህሊና(Consciousness) ራስን ማወቅ(Self Consciousness) የሚሏቸው ነገሮች አሉ።  አንድን  ነገር በማየት ይህ ነገር እንደዚህ ነው ብለን መናገር እንችላለን። በሌላው ወገን ግን በህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ወይም በተጨባጭ የሚታዩ ነገሮችን ለመረዳት በቀጥታ ለማየት ከምንችለው የሚያልፍና ቶሎ ብለን ለመገንዘብ የማንችለው ነገር ነው። ለምን አንድ ህብረተሰብ በዚህ መልክ መዋቀር አለበት? ብሎ የሚጠይቅ አንድም ግለሰብ የለም። ሁላቸንም ስንወለድ ቀድሞውኑ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተዋቀረ ሁኔታ ውስጥ ስለምንወረወርና ስለምናድግ ያደግንበትን፣ ያየነውንና የምንኖርበትን ሁኔታ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን በጥያቄ ውስጥ ሳናስገባ ዝም ብለን ብቻ በመቀበል ከመንፈሳችን ጋር በማዋሃድ በዚያው እንገፋባታለን። የተወለድንበትንና ያደግንበትን ሁኔታ በስርዓት መዋቀሩና ያለመዋቀሩን ቀስ በቀስ በመጠየቅና በመመራመር ወይም ደግሞ ውጭ አገር ለብዙ ዓመታት ስንኖር ጥያቄ ስናነሳና በማነፃፀር ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት የምንችለው። ውጭ አገር የምንኖርበትን ከተማ አገራችን ውስጥ ከተወለድንበት መንደር ወይም ከተማ ጋር ለማወዳደር ደግሞ ያኔውኑ በቀጥታ የሚደረስበት ጉዳይ ሳይሆን ብዙ ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ብቻ ነው። ይህንንም ለማድረግ የምንችለው ወይም ጥያቄ የምናነሳ ሁላችንም አይደለንም። አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በላይ ኖረን በአስተሳሰባችን የማንለወጥ ጥቂቶች አይደለንም። በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካን  ለብዙ አስርት ዓመታት ኖረን ንቃተ-ህሊናችንን ለማዳበር የማንችልና ጥያቄም ለመጠየቅ የማንችል ብዙዎች ነን።

የንቃተ-ህሊናችን መዳበርም ሆነ ያለመዳበር ጉዳይ በልጅነታችን ወቅት በዕድገት ላይ የሚወሰን ጉዳይ ነው። በተለይም በልጅነታችን ወቅት  በነቃና የህብረተሰብን ምንነት በተገነዘበ ቤተሰብ ውስጥ የተወለድንና ያደግን ከሆነ ንቃተ-ህሊናችምም የመዳበርና አስተሳሰባችንም ጥሩ የመሆን ዕድል ያገጋጥማቸዋል። በተጨማሪም የአካባቢው ሁኔታ ለንቃተ-ህሊና በጥሩ መልክ መዳብርም ሆነ አለመዳበር  ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ምን ዐይነት ቤተሰብ ውስጥ እንደተወለድን፣ ምን ዐይነት አስተዳደግ እንደነበረን፣ ጭንቅላታችንን ለማጎልመስ የሚያስችል ዕውቀት ቀስመን ወይም አልቀሰምን እንደሆን፣ በልጅነታችን ብዙ የምንቀሳቀስና ጂምናስትክም የምንሰራ ከሆነ ወይም የማንሰራ ከሆነ፣ በተለይም ደግሞ ከልዩ ልዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ትውውቅ ካለንና ወይም ከሌለን፣ …ወዘተ. ወዘተ. ንቃተ-ህሊናችን የመዳበር ወይም ያለመዳበር ዕድል ያጋጥመዋል። የሳይኮሎጂ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ ማንኛውም ልጅ አመጸኛ ሆኖ አይወለድም። ልጆች ሲወለዱ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። አመጸኛ፣ ወይም ፋሺሽት፣ አሊያም ደግሞ ዴሞክራትና የነፃነት ፈላጊ መሆን በልጅነታችን ከቤተሰብ ከምናገኘው ዕውቀትና አስተዳደግ ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም በምዕራብ አውሮፓ ምድር፣ በተለይም በጀርመንና በጀርመን ተናጋሪ በሆኑት እንደ አውስትሪያ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ምርምር የተደረገበትና በቂ መልስም ለማግኘት የቻለ ነው። ስለሆነም ካደግን በኋላ የሚታየው አስተሳሰባችንና ድርጊታችን በልጅነታችን ወቅት በቀሰምነው አስተዳደግ የሚወሰን ነው። ይህም ማለት የኋላ ኋላ ይህ ዐይነቱ አስተዳደግ በተራ የአካዴሚክስ ትምህርት ሊሻሻል ወይም ሊታረም በፍጹም አይችልም። የስቶይክስ ፈላስፋዎች እንደሚያስተምሩን ከሆነ ተራ የአካዴምክስ ዕውቀት እንዲያውም አስተሳሰባችንን እንደሚያዶለድመው ነው። በሌላ አነጋገር፣ ሰብአዊ ሊያደርገንና በአስተሳሰባችንም አርቆ አሳቢ ሊያደርገን በፍጹም አይችልም።

በተለይም የፈላስፋዎችንና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማራማሪዎችን የህይወት ታሪክ አልፎ አልፎ ላነበበ በልጅነታቸው በቤተሰቦቻቸው ጥሩ እንክብካቤ ስለተደረገላቸውና አስተማሪም ተቀጥሮ ስለተማሩ ነው የኋላ ኋላ ከአገራቸው አልፈው ለዓለም ህዝብ ጠቃሚና ዘለዓለማዊነት ያላቸውን ዕውቀቶች ሊያፈልቁ የቻሉት። ከዚያ በኋላ ራስን በማስጨነቅ ወይም ደግሞ እየመላለሱ በመጠየቅ ነው የበለጠ ተመራማሪና ፈጣሪ ሊሆኑ የቻሉት። በሂደትና ብዙ መጽሀፎችን በማንበብና፣ ተፈጥሮንንም ሆነ የአንድን ህብረተሰብ ሁኔታ በማጥናትና በመቃኘት ሰፋ ያለ ዕውቀትን ማዳበር የቻሉት። ሰልሆነም በጥንት ዘመን አብዛኛዎች ተመራማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ለሰውነታቸው መፈርጠም ሳይሆን ቅድሚያ የሰጡት ስለመንፈስ መጎልመስ ወይም መዳበር ነው። ባጭሩ ለንቃተ-ህሊና መዳበር ነው ከፍተኛ አትክሮ የሰጡት። ምክንያቱም ንቃተ-ህሊናው የዳበረ ሰው በሁሉም አቅጣጫ ስለሚያስብና የሚሰራቸውንም ነገሮች ስለሚያውቅና ራሱንም ስለሚቆጣጠር ብዙ ስህተቶችን አይሰራም፤ ወንጀልም ከመስራት ይቆጠባል፣ ወይም ደግሞ በፍጹም አይቃጣውም። ያም ሆነ ይህ ሰውነታችን ቶሎ የሚጎለምሰውን ወይም የሚፈረጥመውን ያህል ንቃተ-ህሊናችም በዚያው መጠን ይዳብራል፣ የመቃኘት ወይም የማሰብ ኃይሉም ከፍ ይላል ማለት አይደለም። በአካል መጎልመስና በጭንቅላት መዳበር ወይም በንቃተ-ህሊና ከፍ እያሉ መምጣትና ማመዛዘን መቻል አንድ ላይ የሚጓዙ አይደለም።  ለምሳሌ የሰው ልጅ የማቴሪያል ሁኔታዎች እየተሻሻሉ በሄዱ ቁጥር የሰው ልጅም የማሰብና የማመዛዘንም ኃይል እያደገ ሊመጣ ይችላል የሚል ግምት ሊኖረን ይችላል። በሌላ ወገን ግን በመንፈሳዊውና በማቴሪያላዊ ዓለም መሀከል ሚዛናዊነት እስከሌለ ድረስና፣ በተለይም በአሁኑ ቴክኖሎጂ በተስፋፋበትና የቴክኖሎጂ ምርቶችም ዓለም አቀፋዊ በሆኑበትና፣ አብዛኛው ነገር በሚሽብረቀረቅበት ዓለም ውስጥ የመንፈስም መዳበር በዚያው መጠን ሊጓዝ እንደማይችል፣ እንዲያውም እየቀነስ እንደሚሄድ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ይህም ማለት ሰውነታችንን ለመንከባከብ ጥረት እንደምናደርግ ሁሉ ድርጊታችን ከቁጥጥር እንዳይወጣና ሌላውን ላለመጉዳት ከፈለግን መንፈሳችንንም በዚያው መጠን መንከባከብ አለብን ማለት ነው።

ወደ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ ልምጣና እስከዛሬ ድረስ በአገራችን ምድር የደረሱት ችግሮች፣ ወንድም ወንድሙን የመግደል ጉዳይ፣ የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ርስ በርስ መጨራረስና፣ የታሪክን ቅርስ ማውደመና ምርታማና ፈጣሪ ሊሆን የሚችልን ኃይል መጨረስ ወይም መግደል ለዚሁ ሁሉ ነገር ዋናው ምክንያት ጭንቅላት በሚገባ ተኮትኮቶ ያለማደግ ወይም የንቃተ ህሊና ያለመዳበርና ራስን ያለማወቅ ጉዳይ  ነው። ጭንቅላቱ ተኮትኩቶ ያላደገና በየጊዜውም እንክብካቤ እንዲያገኝ አስፈላጊው እርምጃዎች በማይወሰድበት አካባቢ ወይም አገር ውስጥ የግዴታ ከሌላው ላቅ ብሎ የሚገኝ የሚመስለው ግለሰብም ሆነ የህብረተሰብ ክፍል በሌላው ደካማና ራሱን ለመከላከል በማይችለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ በመነሳት ሰቆቃውን ያራዝምበታል። ይህም ማለት በአገራችንም ምድር ሆነ በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለውን ሁኔታና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋውን ጦርነት በምንመለከትበት ጊዜ የጭቆናዎችና የጦርነቶች ዋና ምክንያቶች በሙሉ የመንግስትን መኪና የተቆናጠጡና በዚህም አማካይነት ሀብት ማካበት የቻሉና፣ በየአገሮቻቸው ውስጥም የተስተካከለ ዕድገትና የሀብት ስርጭት እንዳይኖር በሚያደርጉ የኤሊትን ስም የተከናነቡ ጥቂት ኃይሎች አማክይነት ነው። በተለይም ባለፉት አርባ ዓመታት ግሎባል ካፒታሊዝም በፍጥነት እየተስፋፋ በመጣበት ዘመን እንደታሰብውና እንደተገመተው በየአገሮች ውስጥ ያለው ኤሊትና የምሁርን ካባ ያጠለቀው ንቃተ-ህሊናው እየዳበረ ለመምጣት እንዳልቻለ ካለብዙ መጨነቅ መገንዘብ ይቻላል። እንደሚታወቀው የካፒታሊዝም ዋናው ዓላማ በእያንዳንዱ አገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከንቃተ-ህሊና መዳበር ጋር የሚጓዝ የተሰተካከለ ዕድገትን ማምጣት ሳይሆን በየአገሮች ውስጥ በነፃ ገበያ ስም በመግባት ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችንና መፍጠርና ብልግናን ማስፋፋት ስለሆነ በየአገሮች ውስጥ ከመንግስት መኪና ጀምሮ እስከ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ የሚዳረስ አመጽና ብልግና እንዲስፋፉ ይደረጋሉ።  ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ክፍል በተስፋፋበት አገር ውስጥ ደግሞ በባህል፣ በታሪክና በደካማው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ላይም ዘመቻ ይካሄዳል። የሰው ልጅ እንደሰው የማይቆጠርበት ሁኔታ ይፈጠራል። ጥቂቶች ጎልመስውና ደልበው ሲንደላቀቁ አብዛኛው ህዝብ ደግሞ ወደ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ላይ እንዲጣል ይደረጋል። ተፈጥሮም ወደ ተራ ተበዝባዥነት በመለወጥ የብዙ መቶ ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ዛፎች በመቆረጥ የአየር ቀውስ እንዲፈጠር ይደረጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ካለብዙ ጥናትና ፍላጎት የጥሬ-ሀብቶች በመበዝበዝ የአካባቢንና የማህበራዊ ቀውሶች እንዲፈጠሩ ይደረጋል። ይህም ማለት ካፒታሊዝም በአካሄዱና በመስፋፋቱ የተነሳ የስልጣኔ ተልዕኮ(Civilizing Mission) ያለው ሳይሆን  በየአገሮች ውስጥ አመጸኛና ዘራፊ ኃይሎች መፍጠር ብቻ ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ በተለይም የሶስተኛው ዓለም አገሮችን ኢሊቶች ጭንቅላት የሚያደነዝዝ፣ ወደ ውስጥ ራሳቸውን እዳይመለከቱ ወደ ውጭ ደግሞ ተፈጥሮንንም ሆነ በምድር ላይ የሚገኙትን በተበላሸ መልክ ተግብራዊ የሆኑ ነገሮችን ጠጋ ብለው እንዳያዩና ጥያቄ በመጠየቅ መልስ ለማግኘት የማያስችል ኢምፔሪሲዝም(Empericism) የሚባል የትምህርት ስርዓት እንዲስፋፋ በማድረጉ ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ የስልጣኔ ተልዕኮ የሚኖረው፣ ለሰላምና ለተሟላ ዕድገት የሚያስብና ለህዝቡ አለኝታ የሚሆን ኢሌት እንዳይፈጠር በማድረግና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘረጋው የአገዛዝ ሰንሰለት ውስጥ በማካተት ጦርነትን ብቻ ሳይሆን የተዛባ ዕድገትንም ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ቻለ። ይህ ሁኔታ በተለይም ባለፉት አርባ ዓመታት በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ መስፋፋት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ ጥራዝ ነጠቅ ኃይል በመፈጠርና የፖለቲካውን መድረክ በመቆጣጠር ወደ ጨቋኝነት በመለወጥ ዘራፊና አዘራፊ ኃይል ለመሆን በቃ። ይህ ጉዳይ በስልጣን ላይ ያለውን ኤሊት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ገብተው የሚሰሩ በምሁርነትና በአማካሪነት ስም የሚነግዱ ግለሰቦችን ሁሉ በማካተት በአገራችንም ሆነ በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች አመጸኛና ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚያጎበድድ ኃይል ለማፍራት ቻለ። በዚህ መልክ የጭንቅላት አለመዳበር ጉዳይ ወይም የመንፈስ አልባነት ሁኔታ በስልጣን ላይ ያሉትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ሌላውንም ኤሊት ወይም ምሁር ነኝ የሚለውንና ሰፊውንም ወጣት የሚያሳስተውንም የሚመለከት ነው። የንቃተ-ህሊና አለመዳበር ወይም ጉድለት ደግሞ በብሄራዊ ነፃነት መደፈር፣ እ-ሳይንሳዊ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በአሉታዊ ውጤቱ፣ በማህበራዊ፣ በባህላዊና በስነ-ልቦና ቀውስ፣ እንዲሁም በኢኮሎጂያዊ ቀውስና በተበላሹ የከተማ አገነባቦች የሚከሰትና ጠቅላላውን ማህበረሰብ የሚያናጋ ነው። ንቃተ-ህሊናው ያልዳበረ አገዛዝና ሌላው ኤሊት ነኝ ባይ የሚሰሯቸው ነገሮች በሙሉ ለሰው ልጅና  ለአገር ታስበው የማይሰሩ ስለሚሆን ህብረተሰቡ አቅጣጫውን እንዲስት ይደረጋል።  ስለሆነም ሌላውን ትተን ያለፈውን ሃምሳ ዓመታት የአገራችንን ሁኔታ ስንቃኝ በአገራችን ምድር ብሄራዊ ነፃነት ምን ማለት እንደሆን የማያውቅ፣ ህዝባዊ ሀብት እንዴት እንደሚፈጠርና ድህነትም እንዴት እንደሚቀንስ፣ ከተማዎችና መንደሮች ለሰው ልጅ ተብለው እንዴት እንደሚገነቡ የማይገባው ስልጣንን በመቀዳጀትና በደመ-ነፍስ በመመራት አገራችንን ዛሬ የምናያት ሁኔታ ውስጥ ሊጥላት ችሏል።  አብዛኛዎቹ ነገሮች በእልክና በቂም-በቀልነት ስለሚሰሩ አገራችንና ሰፊው ህዝብ የማንም መፈንጫ ለመሆን በቅተዋል ማለት ይቻላል።

በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የተከተለውን ፖሊሲና የአመጽ መስፋፋትና ህብረተሰብአችንን ማዘበራረቅ ወያኔ በጊዜውም ሆነ በዛሬው ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አመጽንና ያልተሰተካለ ዕድገትን ከሚያስፋፋው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር የጠበቀ ግኑኝነትና የእሱም ታዛዥ በመሆኑ ነው። ቀደም ብለው በወጡ አንዳንድ ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ወያኔ በረሃ ውስጥ ሲገባ ዋናው ዓላማው በዚህም በዚያም ብሎ ስልጣን ላይ ለመውጣትና የዘረፋ ፖለቲካ ለማካሄድ እንጂ ለተጨቆነው የትግራይ ብሄረሰብ ዕውነተኛ ነፃነትን ለማጎናጸፍና ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ አይደለም። ወያኔዎችና ተከታይ ካድሬዎቻቸው በሙሉ፣ አንዳንድ ፕሮፌሰሮችም ሳይቀሩ መንፈሳቸው በተሳሳተ ትረካ ስለተሞላ ጥያቄ የመጠየቅና ራሳቸውን የማወቅ ዕድልና ፍላጎትም አልነበራቸውም። ከዕውቀት ጋር ወይም መንፈሳቸውን ከሚያዳብርና ሰው መሆናቸውን ከሚያስገነዝባቸው ልዩ ልዩ ጥበቦች ጋር ዕውቅና ስለሌላቸው ጠቅላላው መንፈሳቸው በአመጽና በመዝበራ የታነፀና፣ እንዲያም ሲል ለኢምፔሪያሊስት ኃይል በማጎብደድና ትዕዛዝ በመቀበል አገራችንን ወደማያቋርጥ የጦርነት አውድማ ለመለወጥ ችለዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነፃ እናወታሃለን ያሉትን ወገናቸውን መቀመቅ ውስጥ ከተዋቸዋል። በማያቋርጥ ጦርነት የተነሳ ቁጥሩ የማይትወቅ ወታት ህይወቱን ሲሰዋ፣ የተቀረው ደግሞ አካለ-ስንኩል በመሆን በሚሽከርከር መቀመጫ(Wheelchair) እንዲሄድና፣ አንዳንዱም በምርኩዝ ብቻ በመደገፍ እንዲንቀሳቀስ ለመደረግ በቅቷል። ለዚህ ሁሉ ድርጊት ዋናውም ምክንያት ጭንቅላት ማንኛውም የሰው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን ባህርይ፣ ማለትም እንደ አርቆ-አሳቢነት፣ ማመዛዘንና፣ የማያቋርጥ ጦርነት ማካሄድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋና ህብረተሰብአዊ መዘበራረቅ ለመገንዘብ አለመቻል ነው። የወያኔዎች ጭንቅላት በአፈጣጠራቸው ማሰብ እንዳይኖራቸው ተደርገው የተፈጠሩ በመምሰል ስራቸው ሁሉ ተንኮል፣ ህብረተሰብን ማዘበራረቅና የማያቋርጥ ጦርነትን ማካሄድ ብቻ ነው። ይህንን ዐይነቱን ኃይል በድርድርና በፖለቲካ ጥበብ ጭንቅላቱን ማስተካከልና እንዲያስብም ማድረግ በፍጹም አይቻልም። እንደነቀርሳ በሽታ እስኪያወድመን ድረስ ተሽክመን የምንዞረው ዕጣችን ነው ማለት ነው።

የዛሬውም የአቢይ አህመድ አገዛዝ የወያኔን ፈለግ የተከተለና፣ ከወያኔ በባሰ ሁኔታ ጦርነትን አጠቃላይና አብዛኛውን አካባቢ እንዲያዳርስ በማድረግ የኦሮሞ ኢሊቶች ነን በሚሉ፣ ይሁንና ደግሞ የማሰብ ኃይል በሌላቸውና የሚሰሩትን በማያውቁ ጥቂት ግለሰቦች የሚካሄድና፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቹ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የአረብ አገሮች የሚደገፍ ነው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ምድር የተፈጠረውን አደገኛ ሁኔታ የሚከታተሉ፣ አዳዲስ ኃይሎች ስልጣን ላይ በወጡ ቁጥር ሁኔታውን ከማብረድ ይልቅ እየተባባሰ መምጣትና፣ ጦርነትም ወደባህልነት የመለወጥን ጉዳይ የሚጠይቁት ጥያቄና የስውን ባህርይ የሚመራመሩ መልስ ለማግኘት የሚጥሩት በአንድ አገር ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ምስቅልቅል ሁኔታና የማያቋርጥ ጦርነት የሚታየው የተወሰነው ኤሊት የማሰብ ኃይ‹ሉ የተሟጠጠ ከሆነና ማንኛውም ሰው በጭንቅላቱ ውስጥ ሊኖረው የሚገቡ ልዩ ልዩ ባህርይዎች፣ ማለትም ራስን ማወቅ፣ ሰው መሆንን መገንዘብራስን ያወቀ ሰው ደግሞ ለሌላውም´ ያስባል. ይፀፀታል፣ አምሳያውን እንደጠላቱ አያየውም፣  የሚሉት መሰረታዊ ባህርዮች የጎደሉት እንደሆን ብቻ ነው። እነዚህ የሰው ልጅ መገለጫዎች የሆኑ ባህርዮች የመንግስትን መኪና በሚቆጣጠረውና በተቀረው ኤሊት ጭንቅላት ውስጥ ስላልተቀረጹ አገርንና ህዝብን የሚያከረባብቱ ለመሆን በቅተዋቅል።  በሌላ አነጋገር፣ ራሱ ሰው መሆኑን የማያውቅ፣ ዝም ብሎ የሚንቀሳቀስ ወይም መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች በመከበብና በመደገፍ ሌላውን የሚያስፈራራና፣ አገሩንም ወደጦርነት አውድማነት ለመለወጥ ደፋ ቀና የሚልና የውጭ ኃይልን ተልዕኮ ለማሟላት መጣደፍ ለዚህ ሁሉ ዋናውም ምክንያት የንቃተ-ህሊና አለመዳበርና በዚህች ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ዋናው ተግባር ምንድነው? ለመጠየቅ ካለመቻል የሚፈጠር አደገኛ ሁኔታ ነው። ባጭሩ መጥፎንም ሆነ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ለመስራትና ለሌሎችም ምሳሌ ለመሆን የምንችለው በጭንቅላታችን ብቻ ነው። ሰውነታችን የጭንቅላታችን ወይም የመንፈሳችን ታዛዥ ስለሆነ፣ ንቃተ-ህሊናችን ሳይዳብርና በጥሩ ዕውቀት ሳይኮተኮት ተግባራዊ የምናደርጋቸው ነገሮች በሙሉ ለማያቋርጥ ስቃይ ዳርገውን ይሄዳሉ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድም የሚተላለፉ ይሆናሉ። በዛሬው ወቅት የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች የሚያነሱትና አትኩሮም የሚሰጡት ነገር የጭንቅላትን ጉዳይ ነው። ይህም ሁኔታ በካፒታሊስት አገሮችም ውስጥ ስለሚታይ የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች የደረሱበት ድምዳሜ የካፒታሊስት አገሮችም ታሪከ-አልባ በሆኑና ጦርነትን በሚናፍቁ ናርስዚስቶች እንደሚመሩ ነው። ስለሆነም የሰውን ልጅና ስልጣኔን እንዳለ የሚያወድሙትንና የሚሰሩትን የአቶም ቦምብ፣ የባዮሎጂና የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችንና እንዳለም አንድን አገር የሚያወድሙ መሳሪያዎችን ስንመለከት እነዚህ ሁሉ የስልጣኔ መገለጫዎች ሳይሆኑ የመንፈሰ-አልባነት መገለጫዎች ናቸው እያሉን ነው የሚነግሩን።

ለማንኛውም በዛሬው ወቅት አገራችን መንፈሰ-አልባ በሆኑ ሰዎች የምትገዛና ህዝባችንም የሚሰቃይበትን፣ የተወሰነው ብሄረሰብ ደግሞ ከውጭ እንደመጣ ጠላት ጦርነት ተዘምቶበት የተወሰነው ሲገደል፣ ሌላው ደግሞ በአካባቢው ሊኖር እንዳይችል የተደረገበትንና የሚሳደድበትን ሁኔታ እንመለከታለን። የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም አማራው በዘለዓለማዊ  ሰቆቃ ውስጥ እንዲኖር የሚያደርጉ ቤተ-መንግስት ውስጥ የሚኖሩ፣ በልዩ መልክ የተዘጋጀ ምግብ የሚመገቡ፤ በመርቼዲስና በቢኤም ደብልዩና በሌሎች የቅንጦት መኪናዎች የሚጓዙ፣ ሱፍ ልብሶችን የሚለብሱና በየቀኑ ሸሚዞቻቸውን የሚቀያይሩ፣ በስማርት ፎን የሚደውሉና ዘመናዊ ለመምሰል የሚሞክሩ፣ ይሁንና ግን በአስተሳሰባቸው ግን እጅግ ወደኋላ በቀሩ ኃይሎች ነው አገራችንና ህዝባችን የሚሰቃዩት። ባጭሩ ኤፍሬም ማዴቦ ላነሳው ጥያቄና እስካሁንም ድረስ እሱም ሆነ ሌሎች ለመመለስ ያልሞከሩት ጥያቄ ዋናው መልስ ከላይ በተቀመጠው መልክ ነው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሰሩ ነገሮች በሙሉ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት በጭንቅላት አማካይነት ስለሆነ ንቃተ-ህሊናው ያልዳበረ፣ በየጊዜው ጭንቅላቱን ለመኮትኮትና ጥያቄም ለመጠየቅ የማይችል ሰው፣ ወይም በኤሊት ስም የሚመጻደቅ በአለባበሱና በአኗኗሩ ዘመናዊ የሚመስል፣ ይሁንና ደግሞ ጭንቅላቱ ባዶ የሆነ ሰው የጦርነትና የምስቅልቅል ሁኔታዎች ዋናው ምክንያት ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም እንደመፈጸም ይቆጠራል። በዚህ ላይ ግንዛቤ ሲገኝ ብቻ ነው በአገራችን ምድር ሰላምና መረጋጋት ሊሰፍኑና ህዝባችንም እፎይ ብሎ ሊኖር የሚችለው። መጽሀፍ ቅዱሱም እንደሚለን፣ ዐይን ሰጥቼሃለሁ በደንብ እንድትመለከት፣ እንድታስብ ጭንቅላት ሰጥቼሃለሁ፣ ፈልግ ታገኛለህ፣ አንኳኳ በሩም ይከፈትልሃል፣ ጥያቄም ጠይቅ መልስ ታገኛለህ የሚሉት መሰረተ-ሃሳቦች በአገራችን ምድር በሚገባ የማይታወቁ በመሆናቸው፣ ቢታወቁም እንኳ ግንዛቤ ያላገኙ ነገሮች በመሆናቸው ራሱ መጽሀፍ ቅዱስንም አነበብኩ፤ ክርስቲያንም ነኝ የሚል ሰው በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል ወንጀል ሲፈጽም ይታያል።

የፓለቲካን ትርጉም ወይም ምንነት ለመረዳት ያለመቻል የሚያስከትለው አደጋ!

በዛሬው ወቅት ሁሉም በየፊናው በፖለቲካ ስም በሚነግድበትና በሚያቅራራበት ዘመን፣ እንዲያም ሲል ካላንዳች መመሪያና ዕምነት በሚተረክበት ዘመን የፖለቲካን ትርጉም ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። በመሰረቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ መጸነስ ከሌሎች ዕውቀቶች ተነጥሎ የሚታይ ነገር አይደለም። ፖለቲካ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ማንኛውንም ግለሰብ የሚመለከት ስለሆነ ከሌሎች ዕውቀቶች፣ ማለትም ከፍልስፍና፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ፣ ከማቲማቲክስ፣ ከሶስዮሎጂና ከኢኮኖሚክስ ሳይንስ ተነጥሎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም በየዩኒቨርሲትዎችም ውስጥ እንደሌሎች የሳይንስ ዘርፎች ፖለቲካም ፖለቲካል ሳይንስ በመባል በትምህርት መልክ ይሰጣል።  የፖለቲካ ሳይንስ ዕውቀት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ ችግርና የሚፈልጋቸውን ነገሮች መፍቻ መሳሪያ ነው። ፖለቲካ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን ጥበብና አንድን አገር በተስተካከለ ዘዴ የማስተዳደሪያ መሳሪያ ነው።

ፖለቲካል ሳይንስ እንደ ሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሚታይ ስለሆነ ማንኛውም የፖለቲካ ሳይንስ የተማረ ሰው የፖለቲካን ትርጉም ይገነዘባል ማለት አይደለም። በተለይም በአለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት ፖለቲካል ሳይንስ ከፍልስፍናና ከሶስይሎጂ ትምህርቶች፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚክስ ሳይንስ ተነጥሎ ስለሚታይ ፖለቲካ ሳይንስና ህብረተሰብአዊ ችግሮችን መፍቻ መሆኑ ቀርቶ ማወናበጃና ሰላምን አደፍራሽ ለመሆን በቅቷል። ስለሆነም በዛሬው ወቅት በአገራችንም ሆነ በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ፖለቲካ ከፍልስፍናና ከሳይንስ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን ሁሉም እንደፈለገው የሚዘባርቅበትና የሚደነፋበት፣ እንዲያም ሲል አንድን አገር የማዋከቢያ መድረክ የሚደረግበት ወይንም ተንኮል የሚሸረብበት ሆኖ ስለሚቆጠር ፖለቲካ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ባህርይውን እንዲያጣ ለመደረግ በቅቷል ማለት ይቻላል። ከዚህ ስነነሳ ፖለቲካ እንደ ተፈጠሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስናና፣ እንጂነሪንግና ሌሎች ለሰው ልጅ የሚያገለግሉ ዕውቀቶች ጋር የሚነፃፀርና ችግርን መፍቻ መሆኑ ቀርቶ ችግርን ፈጣሪ ለመሆን በቅቷል። በመሰረቱ አንድ የፖለቲካ ሳይንስን የሚያጠናና ፖለቲከኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ተፈጥሮአዊ ስጦታ እንዲኖረው ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ወጣት ልጅ ለምሳሌ ፊዚክስ ወይም ማቲማቲክስ ለመማር ተፈጥሮአዊ ስጦታ ከሌለው ዝም ብሎ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ፊዚክስ ወይም ማቲማቲክስ ለመማር ቢፈልግ በጣም ይቸገራል። ተፈጥሮአዊ ሶጦታ ያለው ከሆነ ፍዚክስንም ሆነ ማቲማቲክስን በቀላሉ የመረዳትና የኋላ ኋላ ደግሞ የወጣለት ሳይንቲስት ወይም ማቲማቲሺያን ሊሆን ይችላል። ከዚህ አጭር ማብራሪ ስንነሳ ፖለቲካም የግዴታ ተፈጥሮአዊ ስጦታን የሚጠይቅ ነው። ካለከፍተኛ ግንዛቤና ካለተፈጥሮአዊ ስጦታ ተግባራዊ የሚሆን ፖለቲካ በአንድ አገር ውስጥ ምስቅልቅልን ሁኔታ ይፈጥራል። አገርን ወደ ብልግና መድረክ ይለውጣል። በአሁኑ ዘመን ደግሞ አገዛዙ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በውጭ ኃይል በመታዘዝ ግብረሰዶማዊነትን በህግ እንዲጸድቅ በማድረግ ህዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋል። በዚህ መልክ የተከታታዩ ትውልድ ሞራል እንዲበላሽ ያደርጋል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አንድ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ሰው ብዙ ነገሮችን ማሟለት ይኖርበታል። ካለችሎታውና ከአቅሙ በላይ ፖለቲከኛ ነኝ ቢል የሚያስከትለው ህዝባዊና አገራዊ አደጋ በቀላሉ የሚቀረፍና የሚስተካከልም አይደለም። ስለሆነም ፖለቲከኛ መሆን የሰብአዊነትንም ባህርይ የሚጠይቅና መመሪያም የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። አንድ ፖለቲከኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው መመሪያና ርዕይ እንዲኖረው ያስፈልገዋል። ካለርዕይ፣ ካለደንብ ወይም ካለመመሪያ(Principle) የሚካሄድ ፖለቲካ ፖለቲካ ሊባል አይችልም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲካ እንደ ዕምነት የሚታይና የህዝብ አለኝታ የሚሆንበት ልዩ ጥበብ ነው። በተጨማሪም ፖለቲካ እንደማንኛውም ዕውቀትና የኋላ ኋላ ተግባር ላይ እንደሚውል ሙያ የሚታይ ነው።  በአንድ ሙያ የሰለጠነ ሰው በሚያሳየው የስራ ውጤት የሚመዘነውን ያህል ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ሰው ብቃትነቱን የሚያረጋግጠውውና ተቀባይነት የሚያገኘው ጦርነትን በማካሄድና አገርን በማፈራረስ ሳይሆን አገርን በተሟላ መልክ በመገንባትና ሰላምን በማስፈን ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ መሳሪይ በመታጠቅና በወታደር በመከበብ አገርን የሚያውድምና ህዝብን የሚያስገድል ግለሰብም ሆነ ሌሎች በፖለቲካ ስም የሚመፃደቁ ሰዎች አንድም ቀን ስልጣን ላይ የመቆየት መብት የላቸውም። ከዚህ ሁኔታ ስንነስ ማንም ሰው እየተነሳ ፖለቲከኛ ነኝ ሊል አይችልም። ፖለቲካ ጠብ መጫሪያና፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚደነፋበትና ቂምበቀል የሚወጣበት መሳሪያ ስላልሆነ ፖለቲከኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ራሱን ያዘጋጀና ለዚህም ብቃትነት ያለው መሆኑን የሚጠይቅ ብቻ መሆን አለበት። ስለሆነም ፖለቲካ የራስን ኤጎ ማሟያና ወደ ተራ ቡድናዊነት ስሜት በመለወጥ ተንኮል መተብተቢያ መሳሪያ አይደለም።

ያለፉትን የሃምሳ ዓመታት የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ለተከታተለ ሰው በመሰረቱ በፖለቲካ ስም የተካሄደው ነገር በሙሉ ከፖለቲካ ጋር የሚያያዘው አንዳችም ነገር የለም። ከላይ ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የተለያየ ርዕዮተ-ዓለምን ስም ይዘው ይታገሉ የነበሩ ሰዎችና ድርጅቶች በሙሉ መንፈሳቸው በጥሩ ዕውቀት ያልተኮተኮተና ንቃተ-ህሊናቸውም ያልዳበረ በመሆኑ በተለይም እንደማርክሲዝም የመሳሰሉ በዙ ዕውቀቶችን የሚያካትትና ከፍልስፍናና ከተፈጥሮ ሳይንስና ከሌሎች ዕውቀቶች ጋር በመታከል የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈታ የሚችለው ወደ ተራ አመጽነት እንዲለወጥ በመደረጉ እንዲጠላ ለመደረግ በቅቷል። በጊዜው  የነበረውን የንቃተ-ህሊና ሁኔታና በአገራችን ምድር ይሰጥ የነበረውንም ትምህርት ከማጥናትና በአብዮቱም ዘመን የተፈጠሩት ግብግቦች ከእነዚህ ነገሮች ጋር በጥብቅ የተያያዙ ለመሆናቸው ከማጤን ይልቅ ይህንን ሁሉ ነገር ያመጣብን የማርክሲዝም ወይም የግራ ፖለቲካ ነው በማለት ከፍተኛ ጥላቻ እንዲስፋፋ ለመደረግ በቅቷል። አብዮቱ ከከሸፈ በኋላም በጊዜው በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረው ሁኔታ ከማርክሲዝም ጋር የሚያያዘ አልነበረም ብሎ የሚያስተምር ኃይል ባለመኖሩና፣ በአብዮቱ ወቅት ተዋናይ የነበሩት ኃይሎችና ድርጅቶች በአገራችን ምድር የተፈጠረውን አደገኛ ሁኔታ በሳይንሳዊ ዕውቀት አማካይነት ለማረም ባለመቻላቸው በአሁኑ ወቅት ሁላችንም በመደናበር ላይ እንገኛለን። አንዳች ነገር ቢከሰት እንኳ በምን ርዕዮተ-ዓለምና ፍልስፍና በመታገዝ ነው የተወሳሰቡ የአገራችንን ችግሮች ለመፍታት የሚቻለው ለሚለው ጥያቂ አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ የለም። በሌላ ወገን ግን ሁሉም የዩቱቭ ቻናል እየከፈተ በፖለቲካ ስም ታዋቂ ነን የሚሉ ግለሰቦችን በመጋበዝ የተዘበራረቁ ነገሮች ይነዛሉ።  ባጭሩ የፖለቲካን መሰረተ ሃሳብ ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር ለማብራራትና ለማስተማር የሚችል ኃይል ወይም ቡድን በአሁኑ ጊዜ የለም ማለት ይቻላል።

ከዚህ ሀቅ ስነነሳ አገራችን በፖለቲካ ስም ማንም እየተነሳ የሚጨፍርባትና አገርንና ህዝብን የሚያተረማምስባት አገር ልትሆን በቅታለች። የተለያየ ስምን ይዘው በአገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችና ቡድኖች በራሳቸው ላይ የማይተማመኑና ነፃ አስተሳሰብም ለማዳበር የቻሉ አይደሉም። ሁሉም ማለት ይቻላል ያልተገለጸላቸውና የአገራችውና የህዛበቸው አለኝታ ከመሆን ይልቅ የአሜሪካንን ተልዕኮ የሚያሟሉ ነው የሚመስለው። ሁሉም ማለት ይቻላል፣ በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስ ሳይንስ በመሳሰለው ላይ የጠራ አቋም ያላቸው አይደሉም። በተለያየ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች መሀከል ያለውን ልዩነት የሚገነዘቡ አይደሉም። በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በተከታታይ ተግባራዊ ያደረገውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና መዘዙን ያጠኑና፣ ኒዎ-ሊበራሊዝም ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውንም ጥያቄ በማንሳት መልስ ለማግኘት የሚጥሩ አይደሉም። ዝም ብለው ብቻ በማክሮ ኢኮኖሚክስ ስም ሲያወናብዱ ይገኛሉ። ይህም ማለት ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሊሄድ የማይችልና ተጨባጭ ሁኔታዎችንም ለማስነበብ በማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሰለጠኑ በመሆናቸው ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር የሚያያዘውንና ህብረተሰባዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችለውን የኢኮኖሚክስ ሳይንስ ቦታ ስለማይሰጡና፣ ኢኮኖሚክስ ከብዙ ነገሮች ጋር የሚያያዝና፣ በተለይም ደግሞ ኢኮኖሚክስ ካለፊዚክስ ምንም ትርጉም እንደሌለው ስለማይገነዘቡ ማክሮ ኢኮኖሚክስ የሚለውን ብቻ በማስተጋባት ህብረተሰባችን በድህነትና በረሃብ እንዲሰቃይና፣ በአጠቃላይ ሲታይ አገራችንና ህዝባችን ወደኋላ  እንዲቀሩ ሳያውቁት የስልጣኔውን በር ዘግተዋል ማለት ይቻላል። ስለሆነም በአገራችን ምድር የመንፍስና የባህል አብዮት እስካለተካሄደና አዲስ የተገለጸለት ኃይል ብቅ ማለት እስካልቻለ ድረስ  የጨለማውና የድንቁርናው ዘመን በጣም ይራዘማል ማለት ነው።

ኤፍሬም ማዴቦ ያነሳውን ጥያቄ በበቂው ለመመለስ ከተፈለገ ነቃን የሚሉ ምሁራን ሁሉ መካፈል አለባቸው። ከሁለት መቶና ከሶስት መቶ ዓመታት ወይም ከዚያ በፊት ከነበሩ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች የምንማረው ቁም ነገር አለ። ይኸውም በአውሮፓ ምድር የመጨረሻ መጨረሻ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበላይነትን ለመቀዳጀት የቻሉት የራስን ህይወት መስዋዕት በማድረግ ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ዛሬው ሳይሆን ከሁለት መቶና ከሶስት መቶ ዓመት በፊት በነበሩ ምሁራንና ሳይንቲስቶች መሀከል የአተሳሰብ አንድነት ነበር። በሚያከራክሩ ጉዳዮች ላይ በመከባበር ሃሳብ ለሃሳብ ይለዋወጡ ነበር።  ትግላቸውም ሀቀኛውን መንገድ ለመፈለግ እንጂ በልጦ ለመገኘት ስላልነበረ የመጨረሻ መጨረሻ ቀስ በቀስ ግን ደግም በእርግጠኝነት የተሟላ ዕድገት ሊመጣ ችሏል ማለት ይቻላል። በዛሬው ወቅት ደግሞ የኃይል አሰላለፍ እየተለወጠ በመምጣቱ የተነሳና፣ ፖለቲካውም በመጠላላት ላይ የተመሰረተ ስለሆነና፣ በአሜሪካን የሚመራው የካፒታሊስቱ ዓለም የግዴታ የበላይነትን በሁሉም አገሮች ዘንድ ማስፈን አለብኝ እያለ ስለሚታገልና፣ በየቦታውም የውክልና ጦርነት ስለሚጭር በራሱ በካፒታሊስት አገሮችም ውስጥ አለመረጋጋትና የፖለቲካ መዋከብ እየተፈጠረ ነው። የተለያየ ስም በመያዝ በፖለቲካ ስም የሚነግዱ ፓርቲዎች ከሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ ጋር በመቆላለፍና ሀብትም ለጦር ማምረቻ እንዲሸጋሸግ በመደረጉና ስለሚደረግም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መሀከል መጣጣም አይታይም። በአሁኑ ወቅት ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በራሱ በእያንዳንዱ የካፒታሊስት አገሮችም ውስጥ ጦርነት የሚመጣበትን ሁኔታ እያመቻቸና ለዚህም እየሰበከ ነው። ባጭሩ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም የአገራችንን ሁኔታ ከብዙ አንፃሮች አኳያ  መገምገምና በአገራችን ምድር ሰላምና መረጋጋት ሊሰፍን የሚችልበትን ዘዴና መንገድ ማጥናት ያስፈልጋል። መልካም ግንዛቤ!!

 

                                                                                                                          

                                                                                                                                                                                                                           fekadubekele@gmx.de

                                                                                                                                                                                                                                      www.fekadubekele.com

https://open.spotify.com/show/3Jt5kQGjWEoArsMQSaHBXD?si=a2d25e1f3ca54a90

https://open.spotify.com/episode/1g0XpqN6eoezLkrSZLy3pO?si=f229c703c6e34882

https://open.spotify.com/episode/0UeqMf44TBmsA44FKAYIoO?si=56350fd4524343d6