[gtranslate]

በምርጫ መሳተፍ ወይም ቅስቀሳ ማድረግ ግድያና ውድመት ሲፈጸም ኃላፊነቱን ላልተወጣው አገዛዝ ዕውቅናን እንደመስጠት ይቆጠራል !!

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

ግንቦት 18፣ 2021
መግቢያ
በአለፉት ሶስት ዓመታት በአገራችን ምድር በመንግስትም ሆነ ከመንግስት ጋር በተሳሰሩ ኃይሎች በህዝባችን ላይ ምንም ዐይነት ወንጀል ያልተሰራ ይመስል በሚቀጥለው ወር በሚደረገው ምርጫ ላይ መሳተፍ አስፈላጊ ነው እየተባለ ቅስቀሳ ይደረጋል። አንዳንድ የውጭ ኃይሎችና በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህ ዐይነቱ “ታሪካዊ ምርጫ” እንዳይሳካ አሻጥር በመስራት ላይ ናቸው፤ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና በአሜሪካን ምድር የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምርጫውን ለማሰናከል “ቅስቀሳ ሲያደርጉ” ደርሼበታለሁ በማለት የመንግስቱ የብሄራዊ ደህንነትና መረጃ የሃሰት ወሬ በመንዛት አንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያውያኖችን በማሳሳት ላይ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ተማርን የሚሉና በጥቅም የተገዙ የፕሮፌሰርነትንና የዶክትሬነትን ካባ ያጠለቁ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካን ምድር የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የምርጫውን አስፈላጊነት በማስመር ቅስቀሳ ሲያደርጉ ይታያሉ። የከበርቴው ዲሞራሲ በሰፈነበት በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካን የሚኖሩ ተማርን የሚሉ እንደዚህ ዐይነት ኢትዮጵያውያን ያሉበትን የተደላደለ የኑሮ ሁኔታና የሚያገኙትን ጥቅም በመዘንጋት ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገራችን ምድር ሰላም የሰፈነ ይመስል፣ ግለሰብአዊ ነፃነት እንደነገሰና ህዝባችንም በዲሞክራሲ የተንበሸበሸ ይመስል ለምርጫው መካሄድና አስፈላጊነት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ስንሰማና ስናነብ የእነዚህን ምሁራን ዕውቀትና የማመ´ዛዘን ችሎታ እንድንጠይቅ እንገዳደለን። አንዳንዶች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያስተምሩ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በትላልቅ ኩባንያዎች ተቀጥረው የሚሰሩና በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የሰፈነውን የመናገር፣ ሃሳብን የመስጠትና የመተቸት፣ እንዲሁም ደግሞ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የመሳተፍን ነፃነት የሚያውቁ ናቸው። ይሁንና በአገራችን ምድር በግልጽ የሚታየውን ፖለቲካዊ ጭቆና፣ የሰላም እጦትና ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ከሚኖሩበት አገር የተንደላቀቀ ኑሮ ጋር በማወዳደርና በመጸጸት ከህዝባችን ጎን ሲቆሙ አይታዩም። የእነዚህ ምሁራን የዲሞክራሲ መለኪያ አንድ ሰው ብቻ ነው። በእነሱ ዕምነት የኢትዮጵያ ህዝብ ከቁጥር ውስጥ የሚገባና እንደሰው የሚታይ አይደለም። ዲያቆን ዳንኤልና ፈላስፋው ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በተገኙበት ቤተመንግስት ውስጥ በተደረገ የአድርባዮች ስብሰባ ላይ እዚያው የነበረው አንድ ኢኮኖሚስት “ትላንት ያጣነው መሪ ነበር፣ ዛሬ ደግሞ መሪ አግኝተን ህዝብ አጣን” ያለው አድርባይ አነጋገር በእነዚህ ምሁራንም ዘንድ ሲንፀባረቅ ይታያል።
የለውጥ ኃይል የሚባለው በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ ስልጣንን ከተቀዳጀ ይኸው ሶስት ዓመቱን አስቆጠረ። በእነዚህ ሶስት ዓመታት ውስጥ ህዝባችን በህይወቱ አይቶ የማያውቃቸውን አሰቃቂ ነገሮች በሙሉ ለማየትና ለመቅመስ ተገዷል። በነፃነት ፈንታ ኢ-ዲሞክራሲያዊና አፋኝ ስርዓት ነግሷል። በተለይም ዘር ተኮርና አንድ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ግፍ ተፈጽሟል። አሁን በቅርቡ ደግሞ በመንግስት በተደገፈ በሚመስል በሚገባ በተዳረጀ ኃይል አልጣዬ፣ ሸዋ ሮቢትና ካራ ቆሬ ላይ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ከፖለቲካ ጋር ምንም ዐይነት ግኑኝነት የሌላቸው ምስኪን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በግፍ ተጨፍጭፈዋል። የብዙ መቶ ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠሩ ከተማዎች እንዳሉ ወድመዋል። ቀደም ብሎም ሻሸመኔ፣ በኋላ ላይ ደግሞ መተክልና የምዕራብ ወለጋ እንደዚሁ በየክልሉ አስተዳዳሪዎች የተሰገሰጉና ያንን ከለላ በማደረግ መጤዎች ብለው በሚጠሯቸው ዜጋዎችና ቀይ ፊት ያላችሁ ናችሁ እየተባሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማራዎችና የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች በግፍ ተገድለዋል። በብዙ ሺሆችም የሚቆጠሩም በመፈናቀል ለረሃብና ለብርድ እንዲጋለጡ ተደርገዋል። ይህ ሁሉ ወንጀል ተፈጽሞና አሁንም እየተፈጸመ ባለበት ወቅት ከአገዛዝ ተብዬውም ሆነ ከደጋፊዎቹ ከምርጫ በኋላ አዲስ ሁኔታ እንደሚጠፈር ነው የሚነግሩን። ዛሬ ስልጣንን የጨበጡት ኃይሎች ከምርጫ በኋላ በአሸናፊነት ሲወጡ መልካቸው ሁሉ ተቀይሮ፣ በአዲስ አስተሳሰብ ታንጸው፣ ሙሉ በሙሉ ዲሞክራቶችና የነፃነት፣ እንዲሁም የተሟላ ዕድገት አራማጆች ሆነው በመውጣት አገራችንና ህዝባችንን በተለየ መልክ እንዲሚለውጧት ነው ሊነግሩንና ሊያሳምኑን የሚሞክሩት። “ከምርጫ በኋላ ሁሉንም ነገር ታዩታላችሁ፣ አትቸኩሉ፣ ጊዜ ስጡን” እያሉ ነው ለማዘናጋት የሚሯሯጡት። በተጨማሪም ከምርጫ በኋላና እኛ በአሸናፊነት ስንወጣ እስካሁን ድረስ በግፍ የተገደለው ህዝባችን ከሞተበት በመነሳት ስላማዊ ኑሮ መኖር ይጀምራል፤ አዲሱም አገዛዝ ሁሉንም ነገር ያደርግላቸዋል፣ ብለን እንድንቀበል ነው የሚያጃጅሉን። ይህ ሊሆን እንደማይችልና በምርጫም ብቻ በአገራችን ምድር ምንም ዐይነት ለውጥ፣ መሻሻልና ዕድገት እንደማይመጣ ለማረጋገጥ እሞክራለሁ። ከዚያ በፊት ግን እንደኛ በመሰለው በብዙ ነገሮችና እጅ ወደ ኋላ በቀረው አገርና በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ስለሚካሄደው ምርጫና ስለሚያመጣው ውጤትና በመሀከላችን ስላለው የሰማይና የመሬትን ያህል ዕርቀት ልዩነት ለማሳየት እወዳለሁ። በተለይም በዚህ ነገር ላይ ግልጽ ግንዛቤና አቋም እስከሌለን ድረስ ስለህግ የበላይነትና ስለ ምዕራቡ የካፒታሊስት አገሮች የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ አሰራር መሰረተ-ሃሳቡ አልገባንም ማለት ነው።

የምዕራብ አውርፓ የዲሞክራሲ ዕድገት፣ የፓርቲዎች አወቃቀርና የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ አሰራር!!

በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትንና የብዝሃዊነት ፓርቲ አወቃቀርን ወይም አደረጃጀትን አስመልክቶ በአብዛዎቻችን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጦት አለ። በተለይም እዚህ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካንም ጭምር ከሰላስና ከአርባ ዓመታት በላይ ብንኖርም የፓርቲዎችን መፈጠርና አደረጃጀትት፣ እንዲሁም የሚከተሉትን ርዕዮተ-ዓለምን አስመልክቶ ፖለቲከኞች ነን በሚሉት ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጦት አለ። በአሁኑ ወቅት በአራችን ምርጫ መካሄድ አለበት ብለው የሚወተውቱትንና ለዚህም ቅስቀሳ የሚያደርጉትን ስንመለከት እነዚህ ሰዎች አውሮፓና አሜሪካ ብዙ ዓመታት ቢኖሩም ፓርሊሜንተሪ ዲሞክራሲ በተግባር ሲመነዘር ምን ዐይነት ውጤት እንደሚያመጣ ለመገንዘብ የሚችሉ አይደሉም። በሌላ ወገን ግን በአሁኑ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ምርጫ ቢካሄድ ፋይዳ የለውም፣ እንዲያውም ይባስ ብሎ ለአገዛዙ ዕውቅና መስጠት ነው ብለው የሚሟገቱትን ጽንፈኞች ናቸሁ በማለት የራሳቸውን ኢ-ሳይንሳዊ፣ ፀረ-ዲሞክራሲያዊና ፀረ-ህዝብ አመለካከት በሌላው ላይ ለመለጠፍ ይሞክራሉ። በተለይም ምሁራን ናችሁ ብለው ከሚጠሩን ህዝባችን የሚጠብቀው መሰረታዊ ነገሮች አሉ። አርቆ አሳቢነትን፣ ማመዛዘንን፣ ማነፃፀርንና ተጨባጭ ሁኔታዎችንም ሆነ ፖለቲካዊና መንግስታዊ አወቃቀርን በትክክለኛው የዕውቀት መነፅር በመመርመር ትክክለኛ ትንተና መስጠት። ለሀቅ መቆምና በምንም ዐይነት በጊዜያዊ ጥቅም አለመገዛትና ለዝና ብሎ ህዝብ የጣለብንን አደራ አለመዘንጋት። አንድ ምሁር ወይም የተማረ ሰው ተማረ የሚያሰኘው በራሱ ህሊና ሲገዛና በነፃም ሲያስብ ብቻ ነው። ሀቀኝነትና አንድ ተጨባጭ ሁኔታን በቅጡ መመልከትና ትንተና መስጠት ደግሞ የምሁራዊነት መመዘኛ ነው።
ለማንኛውም ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ የተለያዩ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ለሀቅ ባይቆሙና ትክክለኛው ዕውቀትና መንገድ ይኸኛው ነው ብለው መንገዱን ባያሳዩና አጥብቀው ባይታገሉ ኖሮ በጠቅላላው የሰው ልጅ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንደሚኖር የተረጋገጠ ጉዳይ ነበር። ፖለቲካዊ ፍትሃዊነት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍትሃዊነትና የህግ የበላይነት፣ በተለይም ደግሞ ማንኛውም የሰው ልጅ በአምላክ ምስል የተፈጠረ በመሆኑ በሌላ እሱን በመሰለ መሰቃየት፣ መብቱ መገፈፍና መገደልም የለበትም የሚሉትን መሰረተ-ሃሳቦች ያስተላለፉልንን መሰረታዊ ነገሮች የእነሱን ፈለግ በመከተል ለዕውነተኛ ነፃነትና ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር መታገል ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታችን መሆን አለበት። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ ከሌላ ብሄረሰብ መጣ እየተባለ ጭፍጨፋና መፈናቀል እንዳይካሄድበት አጥብቆ መታገል አስፈላጊ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደነፃ ዜጋ ሲታይና መብቱ ሲከበር ብቻ ነው ዕውነተኛ ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው። ከዚህ በላይ በሁላችንም ዘንድ ከፍተኛ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ የመንግስትን መኪና የጨበጠ ሁሉ ከአምላክ ፈቃድ የተሰጠው ይመስል ህዝባችንን የማሰቃየት፣ የመግደልና መጤ ነህ እያለ የማሳደድ መብት እንደሌለው ነው። ሰውን በጅምላም ሆነ በተናጠል መግደል፣ ከቀዬው ማፈናቀልና ማሳደድ፣ እንዲሁም ከአለአግባብ አንድን ሰው እስር ቤት ውስጥ መወርወር የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚጥሱ በመሆናቸው ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ አመለካከትና ድርጊት ከአገራችን ምድር ለአንዴም ለመጨራሻም ጊዜ መወገድ ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህም አትብቆ መታገል ያስፈልጋል።
በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የዲሞክራሲ ዕድገትና የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ ብቅ ማለት የረጅም ጊዜ የአስተሳሰብ ለውጥና የማቴሪያል ዕድገት ውጤቶች ናቸው። ካፒታሊዝም እንደ ስርዓተ-ማህበር ከመቋቋሙም ሆነ ከመገንባቱ በፊት በከፍተኛ ደረጃ የጭንቅላት ስራ ተሰርቷል። ንቃተ-ህሊና እንዲዳብር መሰረት ተጥሏል። ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ መገንዘብ እንዲቻል ፈላስፋዎች ያልተቋረጠ ጥረት ለማድረግ ሞክረዋል። ምክንያቱም ማንኛውም ነገር በጭንቅላት ስለሚታይ፣ ግንዛቤ ውስጥ ስለሚገባና ስለሚተነተን ነው። ስለሆነም በፍልስፍና ዓለም ውስጥ ጭንቅላት፣ አዕምሮና መንፈስ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ ማለት ነው። ካፒታሊዝም እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣም ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊዳብርና የኑሮ መሻሻልም እንዲኖር ከፍተኛ ትግል ይደረግ ነበር። በተለይም እንደ ሶስዮሎጂ፣ የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎች፣ ታሪካዊ ምርምሮችና፣ የሳይኮሎጂ ምርምር፣ በጠቅላላው የህብረተሰብን ዕድገት የሚመለከቲ ነገሮች በሙሉ ካፒታሊዝም እየተስፋፋና እያደገ ሲመጣ ነው እንደ ዕውቀት መዳበር የቻሉት። ከዚህም በላይ የካፒታሊዝም ማደግና መስፋፋት፣ እንዲሁም አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል እያቀፈ መምጣት ወይም በላቡ እየጣረ እንዲኖር ማድረግ የግዴታ የተቋምም መስፋፋት እንዲፈጠር አስገደደ። በየቦታው ትምህርት ሲስፋፋ ቀስ በቀስም የህብረተሰቡ የማሰብ ኃይል ከፍ እያለ መምጣት ቻለ። ይሁንና ግን እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ወይም ደግሞ እስከ ሃያኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ድረስ በአብዛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የፍጹም ሞናርኪዎች አገዛዝ የሰፈነበት ሁኔታ ነበር። ከሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ በስተቀር ይህንንም ሆነ ያኛውን ዐይነት ስም የለጠፉ ፓርቲዎች አልነበሩም። ዛሬ የተለያየ ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱና ለምርጫም የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ከሰባና ከአርባ ዓመታት በላይ አይበልጥም። እንደ ፖርቹጋልና ስፔይን የመሳስሉት አገሮች ጋ ስንመጣ ደግሞ በእነዚህ አገሮች ፓርቲዎች ብቅ ያሉትና በብዝሃዊነት ላይ የተመሰረተ ፓርላሜንት የተቋቋመው ከ1974 ዓ.ም በኋላ ነው።
ባጭሩ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ፓርቲዎች የካፒታሊዝም እድገት ውጤቶች እንጂ ካፒታሊዝም ከመመሰረቱና ከመዳበሩ በፊት የተፈጠሩ አልነበሩም። ምክንያቱም ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣና አብዛኛውን ህዝብ ተቀጥሮ እንዲሰራ ሲያደርግ ህብረተሰቡ በመደብና በገቢ መከፋፈል ጀመረ። በዚያው መጠንም በአስተሳሰብና በፍጆታ አጠቃቀም እየተለያየ መጣ። ይህ ሁኔታ ፓርቲዎችን በተለያየ የርዕዮተ-ዓለም ስም እንዲደራጁ አስገደዳቸው። ይህንን ወይም ያንን የርዕዮተ-ዓለም ስም የለጠፈ ለዚኽኛው ወይም ለዚያኛውም መደብ ጥቅም ነው እታገላለሁ በማለት በጎራ ተሰለፉ። ስለሆነም የፓርቲዎችም አደረጃጀት ታሪካዊና ህብረተሰብአዊ ግዴታ ነው ማለት ይቻላል። ፓርቲዎችም በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ የተዋቀሩ በመሆናቸው ጠቅላላውን ህዝብ የሚወክሉ ሳይሆን እንደ ርዕዮተ-ዓለማቸው ለዚኽኛው ወይም ለዚያኛው መደብ ጠበቃ የቆሙ ናቸው። ይሁንና ፓርቲዎቹ የርዕዮተ-ዓለም ባህርይ ቢኖራቸውም በአወቃቀራቸው ምሁራዊ ባህርይ ስላላቸውና ከውስጥ በስራ-ክፍፍል በመመደብ የተለያዩ ህብረተሰቡን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማንሳት አንደኛው ሌላውን ቻሌንጅ የሚያደርጉ ናቸው። በፓርቲዎችም ውስጥ የአምላኪነትና የአድርባይነት ባህርይ በፍጹም አይታይም። አንድ ግለሰብ እንደፈለገው አንድን ፓርቲ ሊበውዘውና እኔ በምለው መንገድ ብቻ ተጓዙ የሚል መብት የለውም። አባላቱም በዕውቀት ተወዳዳሪዎች በመሆናቸው አንደኛው ሌላውን ተከታዩ ሊያደርገው በፍጹም አይችልም። መመዘኛቸውም የቆሙለት ርዕዮተ-ዓለማቸውና አንድ ላይ ሆነው ያረቀቁት ፕሮግራማቸው ነው።
በኢኮኖሚ ስርዓቱ ማደግና ተቋሞችና መንግስትም ጭምር ከሞላ ጎደል ዲሞክራሲያዊ አወቃቀር ስላላቸውና በኃላፊነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው በምርጫ አማካይነት አንደኛው ፓርቲ በአሸናፊነት ቢወጣ ተጠያቂነቱ ለጠቅላላው ህዝብ የሚሆንና የተዋቀረውንና በደንብ የሚሰራውን ኢኮኖሚ እንደፈለገው የመለወጥ መብትና ችሎታም የለውም። በህገ-መንግስቱም ስርዓቱን መለወጥ እንደማይቻል የተደነገገ ሲሆን፣ ይህ ማለት ግን አልፎ አልፎ መሻሻሎች አይደረጉም ማለት አይደለም። እንደየ አስፈላጊነቱም ህገ-መንግስቱንም ሆነ ሌሎች ነገሮች ይሻሻሉ። በተለይም በጣልቃ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Interventionist Economic policy) አማካይነትም አንዳንድ የመሻሻያ እርምጃዎች ይወስዳሉ። ካፒታሊዝም በአውቶኖመስ ደረጃ ስለሚሰራም ከምርጫ በኋላ በቂ ድምጽና መቀመጫ ማግኘት ካልተቻለና በአስቸኳይም መንግስት መመስረት የማይቻል እንኳን ቢሆን ስርዓቱ ስራውን አያቋርጥም። ማህበራዊውም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ስራው ይቀጥላል። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ መስሪያቤቶችም ካለምንም ጉድለት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ከብዙ ልምድና የጭንቅላት መዳበር የተነሳም፣ በፓርቲዎች መሀከል ጥምር መንግስት መመስረት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። እስከ 1980ዎቹ ዓ.ም መግቢያ ድረስ በሶሻል ዲሞክራቲክና በሊበራል ፓርቲዎች መሀከል የጣምራ መንግስት የመመስረት ባህል ሲኖር፣ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎችና በሶሻል ዲሞክራቶች መሀከል ከብዙ ድርድር በኋላ የጣምራ መንግስት መመስረት እንደባህልና እንደልምድ እየተወሰደና ተቀባይነትም እያገኝ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ አረንጓዴው ፓርቲ ከሚባለው ጋርም በፌዴራልም ሆነ በሪጂናል ደረጃ በጣምራ መንግስት መመስረት ተለምዷል። በሁለት ፓርቲዎች መሀከል በሚደረገው ድርድርም እስከ ስድስት መቶ የሚቆጠሩ የፓርቲዎች ተጠሪዎች ወይም ጠቅላላውን አባል የሚወክሉ ወካዮች ድምጻቸውን መሰጠትና መሻሻያም ማቅረብ እንደ ቅድመ-ሁኔታም የሚሰራበት መሰረተ ሃሳብ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአንዱ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ወይም ጥቂት ሰዎች እንደፈለጋቸው የሚደነግጉበት ሁኔታ የለም። በፓርሊያሜንቱም ውስጥ እያንዳንዱ ተመራጭ ለህሊናው ተገዢ ሲሆን፣ የራሱን አገዛዝ ፖሊሲ የሚቃወምበት ወይም ድምጽ የሚነፍግበት ጊዜ አለ።
ይህ ጉዳይ አንደኛው ሲሆን፣ በጠቅላላው አገር ውስጥ የህግ የበላይነት የሚባለው በሚገባ የሚሰራበት ነው። በሶስቱም የመንግስት አካሎች፣ ማለትም በህግ አውጭው፣ በህግ አስፈጻሚውና በኤክስኩቲቩ መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ ክፍፍል አለ። ስልጣንን የጨበጠው ኃይል ወይም ኤክስኩቲቩ ከፓርሊያሜንቱ በስተጀርባ ወይም እሱን በመርገጥ የፈለገውን ነገር ለማድረግ አይችልሞ፤ መብትም የለውም። የፓርሊያሜንታሪ አጣሪ ኮሚቴ የሚባል ነገርም ስላለ አንዳንድ ሚኒስተሮችና አገዛዙ ራሱ ከህገ-መንግስቱና ከፓርቲዎች ስምምነት ውጭ በራሳቸው ፈቃድ አንዳንድ ስምምነቶችን ካደረጉ በቀጥታ ይጠየቃሉ። እንደሁኔታውም ፓርሊያሜንቱ በመሰብሰብ በጠቅላይ ሚኒስተሩ ላይ ዕምነት እንደሌለውና(Vote of no Confidence) ድምጽም በመሰጠት በድምጽ ብልጫ ከስልጣን የሚነሳበት ጊዜ አለ። ተግባራቸውንም በሚገባ የማይወጡ ሚኒስተሮች ክስልጣናቸው በአስቸኳይ እንዲነሱ ይደረጋሉ። ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ዋናው ጉዳይ የመንግስቱ መኪናና ከምርጫ በኋላ ስልጣንን የሚጨብጠው ፓርቲ አንድ ላይ የሚያያዙና ገዢው ፓርቲ እንደፈለገው የመንግስቱን መኪና የሚጠመዝዘውና ለጥቂት ሰዎች መገልገያ የሚያደረገው ሳይሆን የመንግስቱ መኪና በአውቶኖመስ ደረጃና በህገ-መንግስቱ መሰረት የሚሰራ ነው። ይህም ማለት የመንግስቱ መኪና፣ ማለትም ወታደሩ፣ ፖሊሱ፣ የስለላ ድርጅቱ እንደመጨቆኛ መሳሪያ የሚታዩ ሳይሆን የህዝብን ደህንነት የሚጠብቁ ናቸው። ሰላማዊ ሰልፍ ቢደረግና ሰልፉም ከቁጥጥር ውጭ ቢወጣ በህዝብ ላይ የመተኮስ መብት የላቸውም። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ደግሞ በህገ-መንግስት ፍርድ ቤት(Constitutional Court) ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልጣን የጨበጠውን ፓርቲ ወይም የጣምራ አገዛዝ የመክሰስ መብት አላቸው። ለምሳሌ አገዛዙ የሚወስደው ማንኛውም ፖሊሲ ከህገ-መንግስቱ ጋር የማይጣጣም ከሆነ አገዛዙ ይከሰሳል። ከዚህም በላይ በፓርላሜንት ውስጥ በድምጽ ብልጫ የጸደቀ ህግ በህገ-መንግስት ፍርድ ቤት ሊሻርና በሌላ ሊተካ ይችላል። ስልጣንን የጨበጠውም ፓርቲ የህገ-መንግስቱን ውሳኔ አልቀበልም የማለት መብት በፍጹም የለውም። ከዚህ ውጭ ደግሞ መንግስትንም ሆነ ፓርቲዎችን የሚቆጣጠሩ በደንብ የተደራጁ የሲቪል ማህበረሰብ አሉ። እነዚህ ራሳቸው በመንግስቱ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ጫናና መሻሻልም እንዲደርግ ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ በመንግስት በጀት ተመድቦላቸው የአገር ውስጥንና የውጭውን ፓለቲካ፣ የህበረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ጉዳይ፣ የስነ-ምግባርን ጉዳይ በሚመለከት…ወዘተ. ምርምርና ጥናት በማድረግ ለመንግስት የሚያቀርቡና ምክርም የሚስጡ አሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ ቢያንስ ከስድስት በላይ የሚሆኑ የኢኮኖሚክስ የምርምር ተቋማት አሉ። እነዚህም በርዕዮተ-ዓለም ወይም በተለያየ ሳይንሳዊ አመለካከት የተደራጁ በመሆናቸው የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ በማጥናትና በሰው የገቢም ሆነ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ በመመርመር ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለመንግስት ምክር ይሰጣሉ፣ በመንግስትም ላይ ግፊት ያደርጋሉ። በልዩ ልዩ ተቋማት የሚደገፈው የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በዚህ መልክ የሚሰራና ህብረተሰብአዊ መረጋጋት እንዲኖር የሚያደርግ ነው።
ባጭሩ በሰለጠነው የምዕራቡ ዓለም የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ አሰራሩ እንደዚህ ነው። ፓርቲዎችም የአድርባይነት ባህርይ በፍጹም የላቸውም። ዕምነታቸውም ለቆሙበት ዓላማ ሲሆን አብዛዎችም ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸውና ኃላፊነትም የሚሰማቸው ናቸው። ይህ ዐይነቱ የዳበረ አስተሳሰብ ለመቻቻል፣ ችግሮችን በውይይትና በክርክር፣ በተለይም በዕውቀት ደረጃ እንዲፈታ አስችሎአቸዋል። ስለሆነም ነው መረጋጋት የሚታየውና፣ አንድ ዐይነት ችግርም ሲከሰት በአስቸኳይ መፍትሄ ለመፈለግ ሩጫ የሚደረገው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በኋላ ሁኔታዎች በዚህ መልክ መቀጠል እንደማይችሉ በመረዳታቸው የወደፊቱን ሁኔታና ሊከሰት ከሚችለው ሁኔታ ጋር ሊሰራ የሚችል ምርምር እያደረጉ ነው። ብቃትነት ካላቸውና በመንግስት ከሚደጎሙት ተቋማት ባሻገር ከሁለት መቶ በላይ በተለያየ ፊልድ የሰለጠኑ ምሁራንን ያቀፈ ተቋም በማቋቋም ጥናትና ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። የወደፊቱም ኢኮኖሚ አደረጃጀት የምርትን አመራረት፣ የጥሬ-ሀብትን ሁኔታ፣ የአየር መለዋወጥን ጉዳይ በማጤን ጠቅላላው ስርዓት ተከታታይነት (Sustainability) እንዲኖረውና ለተከታታዩ ትውልድም እንዳያልቅ ታስቦ በመዘጋጀት ላይ ነው። እንደኛው አገር በአቦ ሰጡኝ የሚሰራ አይደለም ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ነው በአገራችን ምድር በተለይም በአሁኑ ሁኔታ የምርጫን አስፈላጊነትና አላስፈላጊነት፣ እንዲሁም ከምርጫው ውጤት ህዝባችን የሚጠብቀውንና የሚፈልገውን ማግኘት ይችል እንደሆን መመርመር የምንችለው። ዋናው መሰረተ ሃሳብና በጭንቅላት ውስጥ መቋጠር ያለበት ጉዳይ በአውሮፓ ምድር ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ስልጣን ላይ የያዙትና አገሮቻቸውን በጊዜው ከሰፈነው ከፍተኛ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የባህል ቀውስ ሊያላቅቁ የቻሉ መሬዎች በጀርመን እንደ አደናወር፣ በኋላ ደግሞ ዊሊይ ብራንዳትና ሄልሙት ሽሚድት ሲሆኑ፣ በአውስትርያ ብሩኖ ክራይስኪ፣ በስዊድን ደግሞ ኦላፍ ፓልመ የሚባሉት ታላላቅ መሪዎች ናቸው። እነዚህ በጊዚው የየአገሮቻቸው መሪዎች ብቻም ሳይሆኑ የዓለም መሪዎችም ነበሩ ማለት ይቻላል። በትልቅ ታታሪነት፣ አስተዋይነትና ቻይነት አገሮቻቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከደቀቀ ኢኮኖሚ በማላቀቅ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባት እኛም መጥተን እዚህ ለመኖር እንድንችል አድርገዋል። መሪ ማለት እንደዚህ ነው እንጂ በተንኮል መንፈስ በመጠመድ የራሱን ዜጋ በመግደልና በማስገደል አገሩን መቀመቅ ውስጥ የሚያስገባ አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግስታዊ አወቃቀር ለዲሞክራሲ እንቅፋት የመሆኑ ጉዳይ!

በአገራችን ምሁራን ዘንድ የመንግስትን መኪና አወቃቀርና ተግባር አስመልክቶ አንዳችም ቦታ ጥናትና ምርምር ተደርጎ አያውቅም። ስለዚህም ጉዳይ ማንሳት እንደወንጀልና እንደ አናርኪስነት ነው የሚያስቆጥረው። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት መንግስት የሚባለው ነገር ከእግዚአብሄር የተሰጠ፣ በሂደት ውስጥ መሻሻል የሌለበት፣ የማይነካና የማይዳሰስ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ስለሆነም መንግስት ዲሞራሲያዊ ባህርይ ሊኖረው አይገባም፣ ስልጣንንም የሚጨብጡ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የዕውቀት ብቃት ሊኖራቸው አይገባም። ማንም ሰው እየተነሳ የመንግስትን መኪና በመጨበጥ የፈለገውን ነገር የማድረግ መብት አለው የሚል ግንዛቤ በአብዛኛዎቻችን መንፈስ ውስጥ ተቀርጿል። መንግስት አገለጋይና ህዝቡን ከማንኛውም አደጋ ጠባቂ ሳይሆን ከላይ ሆኖ የሚያዝና በፈላጭ ቆራጭነት የሚገዛ ነው። ይህ ዐይነቱ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ነው እስከዛሬ ድረስ አገራችንን መቀመቅ ውስጥ የከተታትና ህዝባችንም ፍዳውን እንዲያይ የተደረገው።፡
በሌላ ወገን ግን በአውሮፓ የካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ ከመንግስት መኪና አንስቶ እስከሌሎች ጉዳዮች ድረስ ምርምርና ክርክር ሳይደረግ አንዳችም ነገር በፍጹም ተግባር ላይ አይውልም። መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? ተግባሩስ ምንድነው? ምን ዐይነት ሰዎችስ የመንግስትን መኪና መቆጣጠር አለባቸው? ስለሆነም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሰውን ልጅ ህይወት የሚመለከቱ ማንኛውም ነገሮች፣ ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍትሃዊነትን አስመልክቶ ሰፋ ያሉ ምርምር ተካሂዷል። ከተማዎች እንዴት እንደሚገነቡ፣ የቤቶች አሰራር ምን ዐይነት ይዘት እንደሚኖራቸው፣ በተፈጥሮና በሰው ልጅ መሀከል ሊኖረው የሚገባው ግኑኝነት… ወዘተ. ደረጃ በደረጃና በጥልቀት ተመርምረዋል። በዚህም መሰረት ተግባራዊ ሊሆኑ በቅተዋል። ይህም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ በጣም አስከፊ ሁኔታና ጨቋኝ አገዛዞች ስለነበሩ ይህንን በጥብቅ የተመለከቱ ምሁራን አንድ ህዝብ እንደ እንስሳ መታየት የለበትም፣ አንድ አገርም በዚህ መልክ ሊያድግ አይችልም፣ ማህበራዊ ሰላምም ሊኖር አይችልም ብለው በመረዳታቸውና የህግ የበላይነት መከበርንና የመንግስት ተግባርንና ኃላፊነትን በሚመለከት በግልጽ እንዲታወቅ አጥብቀው በመታገላቸው ነው። ይህ ያልታከተ ትግላቸውና ምርምራቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ቀስ በቀስ ተግባራዊ መሆን በመቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ መንግስት የካፒታሊዝምን ዕድገት አራማጅ እንዲሆን ሆኖ በመዘጋጀት ቀስ በቀስ በእርግጥም ደግሞ ጠቅላላው ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴኮኖሎጂ ላይ ተመስርቶ እንዲቀሳቀስ አስችሎታል። ይህ ማለት ግን ከሶስት መቶና አራት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ፈላስፋዎችና የተፈጥሮ ሳይንቲስቶች ምኞት ካፒታሊዝምን እንደ ስርዓተ ማህበር ተግባራዊ ማድረግ ሳይሆን ጥበባዊና ስርዓት ያለው፣ እንዲሁም በሁሉም አቅጣጫ ፍትሃዊነት የተሞላበት ስርዓት መመስረት ነበር። የኋላ ኋላ እነሱ የተመኙት ሳይሆን በአሸናፊነት የወጣው ዛሬ ካፒታሊዝም ብለን የምንጠራው ስርዓት ነው። ይሁንና ከብዙ ልምድና ትግል በኋላ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መሻሻሎች በመደረጋቸው በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ልዩ ልዩ ድጎማችዎችን እንዲያገኝ ተደርጓል።
ወደ አገራችን ስንመጣ የአገራችን ዘመናዊ የመንግስት መኪና አወቃቀር የምሁራዊ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚው ማደግ፣ የከተማዎች መገንባትና በተለያዩ መገናኛና መመላለሻ መንገዶች መያያዝ ነፀብራቅ ወይም ውጤት አይደለም። የአገራችን ዘመናዊ የመንግስት መኪና አወቃቀር ከውጭ የመጣና ወደ ኋላ በቀረ ስርዓትና አስተሳሰብ ላይ የተጫነ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ መንግስታዊ አወቃቀር እንደ ካፒታሊስቱ የመንግስት መኪና አወቃቀር ኢኮኖሚው ሰፋ ባለ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ ተመስርቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ ሳይሆን እንዲያውም ካፒታሊዝም እንዳያድግ የሚያፍንና፣ ሰፊው ህዝብ ባልባሌ ቦታዎች ላይ እንዲሰማራ የሚያደርግ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለሃይማኖትና ለጎሳ ግጭት ምክንያት ሊሆን ችሏል። ኢኮኖሚያዊ መዛባት፣ ኢኮኖሚው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተደግፎ ለመንቀሳቀስ አለመቻል፣ ሰፋና ግልጽነት ያለው የገበያ ኢኮኖሚ አለመኖር፣ ሰፊው ህዝብ ተከታታይነት ያለው ገቢ እንዲኖረው አለመደረጉ፣ የወጣቱ በስራ መስክ መሰማራት አለመቻልና የሙያ ማስልጠኛ ቦታዎች ባለመኖራቸው ጊዜውን ባልባሌ ነገሮች ላይ እንዲያሳልፍ መደረጉ…ወዘተ. …ወዘተ. እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ለማህበረሰባዊ ግጭቶች፣ በጎሳዎችና በሃይማኖቶች መሀከል ላሉ መሻከሮች ምክንያት በመሆን ግጭት እንዲፈጠሩ የማድረግ ኃይላቸው ከፍ ያለ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ አደገኛ አጀንዳ ላላቸው ለውስጥና ለውጭ ኃይሎች በጣም አመቺ ነው። ህብረተሰብአዊ ግጭት እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ስለሆነም አገዛዝ የሚባለውና የመንግስቱ መኪና በጣም ጠባብ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች በመያዛቸው በህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ሁሉ የመመልከት ኃይል የላቸውም። ግጭት ሲፈጠር ሁኔታውን ለማረጋጋት የሚሞኩሩት በጠብመንጃ ወይም በመተኮስና ሰውን በመግደል ነው። በመሆኑም ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች እንደ ባለስልጣን የሚታዩ ወይም የመንግስት መኪና የግል-ሀብታቸው አድርገው የሚቆጥሩ እንጂ እንደ ህዝብ አገልጋይና አገርን አሳዳጊና ብሄራዊ ነፃነትን አስከባሪ ሆነው የሚታዩ አልነበሩሞ፤ አይደሉምም። ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስታተስ በመዝናናት በመደሰት ህዝብን የሚንቁና አገርን ለውጭ የስለላ ኃይሎች አሳልፈው የሚሰጡና፣ አሁንም የሚሰጡ ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ሰፋ ያለና የተገለጸት ምሁራዊ ኃይልም ባለመኖሩ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ህዝባችንን እንዲገዙ ከአምላክ የተላኩ መስለው ስለሚታዩ የጥሬ-ሀብት በተትረፈረፈበት አገር ውስጥ ህዝባችን በድህነትና በረሃብ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተደርጓል። የመጨረሻም መጨረሻም ዛሬ እንደምናየው የጦርነት ሰለባ በመሆን ፍዳውን እያየ እንዲኖር ተገዷል።
ስለሆነም በየጊዜው ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ቀድሞ የተዋቀረውን የመንግስት መኪና ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ የባሰውኑ የጭቆናውን መሳሪያ በማጠናከር ህዝባችንን ረግጠው እንዲገዙ አስችሎአቸዋል። ከየካቲቱ የስድሳ ስድስት ዓ.ም አብዮት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የመንግስቱ መኪና ትናንሽ ጭንቅላቶች ባላቸው ወይም መንፈሰ-አልባ በሆኑ ሰዎች የተያዘና የመንግስትን ሚና ባልተረዱ የሚበወዝና ንጹህ በንጹህ የካፒታሊዝምን ዕድገትንና፣ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብር እንቅፋት የሆነ ነው። ስልጣንን የጨበጡ ሰዎች፣ ስለጥበብ አስፈላጊነትና ማህበራዊ ሚና፣ ስለ ሙዚቃ የሰውን መንፈስ አዳሽነትና አረጋጊነት፣ ስለሙዚየሞች መሰራት፣ ጥበባዊ የሆኑ ህንፃዎች ስለመሰራታቸው፣ ባጭሩ አንድ ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ ተከታታይነት እንዲኖረው ምን ምን ነገሮች ከታች ወደላይ መሰራት እንዳለባቸው የሚያውቁት ነገር ስለሌለ አገራችንን በመጨቆኛ መሳሪያ ኃይል ብቻ ነው የሚገዙት። ይህ ዐይነቱ መንግስታዊ አውቃቀር ያለውን ኋላ-ቀርነት የባሰውኑ የሚያጠናክርና ህዝቡን አቅመ-ቢስ የሚያደርግ ነው። ድንቁርናን የሚያስፋፋና ያለውንም የሚያጠነክር ነው። ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች በሙሉ በጭንቅላታቸው የሚያስቡ ባለመሆናቸው የመንግስትን መኪና የሚጠቀሙበት ህዝብን ለማገልገልና አገርን ታላቅ ለማድረግ ሳይሆን የራሳቸውን ዘመዶች ለመጥቀም ብቻ ነው። በአብዛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሰፈኑትን ወይም የተዋቀሩ መንግስታትን አስመልክቶ በተገለጸላቸው የአውሮፓ ምሁራን በሰፊው የተጠናና የተተነተነ ነው። ይሁንና ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚቅበጠበጠው የአገራችን ምሁር ጠጋ ብሎ ከመመርመርና ከማጥናት ይልቅ በአጉል የኩራትና የጉራ ስሜት ወደፊት በመገስገስና ከአንዳንድ መልካም አስተሳሰብ ካላቸው ኢትዮጵያውያኖች የሚመጣውን አስተያየት ላለመስማት በመፈልግ በዚህና በሌሎች አያሌ ነገሮች ላይ ጥናትና ክርክር እንዳይደረግ በማድረግ ለዕድገት እንቅፋት ለመሆን በቅቷል። አሁንም በየቦታው የሚደረገውን የዙም ውይይት ሳዳምጥ በአብዛዎች ዘንድ የቱን ያህል ኋላ-ቀርነት እንደነገሰ ለመገንዘብ ችያለሁ። አብዮቱ ከፈነዳ ከአርባ ዓመት በኋላም በአተሳሰባችን አልተሻሻልንም። ሁሉም በየፊናው ስልጣንን በመጨበጥ እንዴት አድርጌ ያንን ምስኪን ህዝብ ማሽትና የውጭ ኃይሎችን ማገልገል እችላለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ እንጂ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚና ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግስታዊ መኪና በማዋቀር አንድ ታላቅ አገር ለመገንባት አይደለም የሚታገል የሚያስመስለው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በህወሃት ዘመንም ሆነ በዛሬው ዘመን በህዝባችን ላይ የሚወርደው ሰቆቃና ግድያ ይህን ያህልም የሚያስገርም አይደለም። ተራ የአካዳሚ ዕውቀትም ጭንቅላታችንን በማለስለስ ለስልጣኔ እንድንቆም አላደረገንም። አንዳንዶች መልካቸው የሚያማምሩ ቢመስሉም ጭንቅላታቸው ውስጥ ሰይጣን ያለ ይመስል የባሰውን አረመኔ መሆናቸውን እያረጋገጡልን ነው። ሲግሙንድ ፍሮይድ አንድ ቦታ ላይ እንዳለው በፊዚካል ውበትና በአስተሳሰብ ወይም ደግሞ በንቃተ-ህሊና መሀከል መጣጣም ሊኖር አይችልም፣ ወይም ደግሞ አንድ ሰው ቆንጆ በመሆኑ የግዴታ በባህርይውም ቆንጆ ይሆናል ብሎ መገመት አይቻልም ያለው በአገራችን ምድር በግልጽ የሚታይና የሚረጋገጥ ሀቅ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ባለስልጣናት ጭንቅላታቸው ወይም አስተሳሰባቸው በመልካቸው ስለሚሸፈን የማሰብ ኃይላቸው ይቀጭጫል። ለጭንቅላታቸው መዳበርም ይህን ያህል ትኩረት ስለማይሰጡ የበለጠውን ወደ አረመኔነት በመለወጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ ህይወት ያበላሻሉ። ታሪክንና ባህልን እንዳለ ያወድማሉ። የመጨረሻ መጨረሻም አንድ አገር በውጭ ኃይሎች እንድትወረር ሁኔታውን አመቻችተው ይሄዳሉ።
ስለሆነም በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥና የመንግስት አወቃቀር ምርጫ ማካሄድ ያለውን ኋላ-ቀርነትና የተዝረከረከ አኗኗር ዘዴ የባሰውኑ የሚያጠነክር እንጂ ተዓምር ሊፈጥር አይችልም። በአገራችን ምድር መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ መንግስት በሚባለው መሰረተ-ሃሳብ ላይና ዲሞክራሲያዊ ባህርይ እንዲኖረው ስለመደረጉ ጉዳይ በጥልቅና በስፋት መወያየት ያስፈልጋል። በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ክርክር ማድረግ አለብን። አሰልቺ ከሆኑ ታሪካዊ ሀተታዎችና፣ አገራችን እንደዚህ ነበረች ከሚለው አባባል መላቀቅና ለዕድገትና ለስልጣኔ በሚያመቹ ነገሮች ላይ ብቻ መወያየትና ማጥናት አለብን። አይ ይህ አያስፈልግም፣ የሚያስፈልገው የሰዎችና የህገ-መንግስት መለወጥ ብቻ ነው የምንል ከሆነ ከአሁኑ ባይ ባይ ኢትዮጵያ ብለን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ አለብን።

የፓርቲዎች አደረጃጀት ድክመትና እንዲሁም ለኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት የመሆን ጉዳይ!!

ትላንትም ሆነ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ፓርቲ አለን፣ ተደራጅተናልም ብለው ለስልጣን የሚታገሉትን፣ ወይም ለምርጫ እንወዳደራለን የሚሉትን ፓርቲ መሰል ነገሮች ስንመለከት የደቀቀ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ምሁራዊ መሰረት የሌላቸውና አንድ አገር እንዴት ከታች ወደላይ (Organically) እንደሚገነባና ህዝቡም እንደማህበረሰብ እንዴት መተሳሰር እንዳለበት የሚያውቁት አንዳችም ነገር የለም። ስለሆነም ስልጣን ቢጨብጡም በመጀመሪያ ደረጃ ምን ምን ነገሮች ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው የተረዱና ለመረዳትም የሚፈልጉ አይደሉም። ባለው የተጨማለቀ ነገር ላይ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የስራ መስክ ከመክፈትና ድህነትን ከመቅረፍ ይልቅ ያለውን ሁኔታ የሚያባብሱ ይሆናሉ። በተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መሀከል ያሉትን ልዩነቶች ስለማይረዱ በቀላሉ በዓለም አቀፍ ተቋማት በመመከር የባሰውኑ ድህነትን የሚያመጡና ሀብት እንዲባክን የሚያደርጉ ይሆናሉ። በአገራችን ያለው የፓርቲዎች ድክመት የምሁሩም ድክመት ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል። ምሁሩ ከራሱ ወጣ ብሎ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ዝግጁ ያልሆነና ፍላጎትም ያለው አይደለም። ሰነፍና ባለው ዕውቀት ስለሚዝናና ምሁራዊ ብስለት እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። አስተሳሰቡና አካሄዱ በሙሉ ለዕድገት እንቅፋት ነው። ለማዳመጥ፣ ለመከራከርና ለማስተማር ዝግጁ አይደለም። አብዛኛውም ምንም ዐይነት አቋም የለውም። በሌላ ወገን ደግሞ ዛሬ ለስልጣን እንወዳደራለን ብለው ከተመዘገቡት ውስጥ አንዳንዶችም ሆነ ውጭ አገር ሆነው የሚጮሁት በአንድ ወቅት ወንጀል የሰሩና ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ያሰቃዩ የነበሩ ናቸው። በአውሮፓ ፓርቲዎችም ሆነ በምሁራን ታሪክ ውስጥ አቋመ-ቢስ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የለም። ሁሉም ለቆመበትና ላመነበት ዓላማ የሚታገል ነው። በደም ፍላትና ሌላውን በመወንጀል የሚራወጥ ሳይሆን በሳይንሳዊ ግንዛቤ የራሱን ትንተና ለመስጠት የሚሞክር ነው። የአገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምሁሩን አስተሳሰብ በምንመረምርበት ጊዜ አብዛኛው በመጯጯህ ጊዜውን የሚያባክን እንጂ አቋሙን በጽሁፍ ለማስረዳት የሚሞክርና በክርክር ለማሳመን የሚጥር አይደለም። ይህንንም ሆነ ያኛውን ፓርቲ ወይም ግለሰብ እንደግፋለን የምንልም በራሳችን ዕምነትና አስተሳሰብ የምንመራ ሳንሆን የምንነዳና በቀላሉ የምንኮራረፍ ነን። ስራችን ሁሉ እንድንፋጠጥና እንድንጨራረስ የሚያድርግ ነው። መንፈሳችን የተረበሸና ወደ ቂም በቀል የሚያደላ ነው። ስለሆነም ስልጣንን የሚጨብጥ ኃይል ሁሉ ከምሁራዊ አስተሳሰብና ብስለት በመነሳት ሳይሆን ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን ተግባራዊ የሚያደርገው ተበድዬ፣ ተጨቁኜና ተዋርጄ ነበር በማለትና ተገርፎ እንዳደገ ሰው የተራዬን ቁጭቴን መወጣት አለብኝ በማለት ነው። በመሆኑም ፖለቲካ የቂም በቀል መውጫ፣ የተንኮል መስሪያ፣ አገርንና ባህልን ማከረባበቻና የመጨረሻ መጨረሻም የሚቀናቀነውን ሁሉ ማጥፍያ መሳሪያ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። በእነዚህ ዐይነት ሰዎች ዕምነት ፖለቲካ ከሞራል ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፣ ወይም ደግሞ ስለሞራል የሚያውቁት ነገር የለም። ይህ ዐይነቱ ደመ-ፍላት በከፍተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ መገታትና መድረኩ የግዴታ ሰፋ ላለ ለፍልስፍና፣ ለቲዎሪና ለሳይንስ ክርክር ክፍት መሆን አለበት። የአንድ አገር ችግር በአጉል ትረካ የሚፈታ ሳይሆን በሳይንሳዊና በፍልስፍናዊ የአነባበብና በቲዎሪ የአተናተን ዘዴ ብቻ ነው። ትክክለኛ ፍልስፍናና ሳይንስ መመሪያችን ሲሆኑ ብቻ ነው ተጨባጭ ሁኔታዎችንም ማንበብ የምንችለውና በተጨባጭ ለሚታየው ችግርም ተቀራራቢ መፍትሄ ማቅረብ የምንችለው። ይህ ዐይነት ሁኔታ በሌለበት አገር ውስጥ የአገራችን የተወሳሰበ ችግር በተራ ምርጫ ብቻ ሊፈታ ይችላል ብሎ መገመት የዋህነት ነው።
ለምርጫ እንወዳደራለን ብለው በምርጫ ቦርዱ የተመዘገቡትን የፓርቲዎች የሞራል ብቃት ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛዎቹ ምንም ዐይነት የሞራል ብቃት ያላቸው አይደሉም። በመጀመሪያ ደረጃ በአገራችን ምድር እየኖሩ በምድር ላይ የሚታየውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ማንበብና መተንተን የሚችሉ አይደሉም። ህዝባችን በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖር በየቦታው እየተንቀሳቀሱ የሚጎበኙ አይደሉም። በእግራቸው ስር ያለውንና የሚታየውን ነገር እንኳ ማየት የማይችሉና ጥያቄም ለማቀረብ መንፈሳቸው የተዘጋጀ አይደለም። በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ አብዛኛው ህዝብ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መኖሩ እየታወቀ እየተዘዋውሩ በማየት ኗሪው ህዝብ ከዚህ ዐይነት አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለወጥ ሊመጣ የሚችልበትን መንገድ ሲወያዩና በመንግስትም ላይ ግፊት ሲያደርጉ አይታይም። ከዚህም ባሻገር በዶ/ር አቢይ የተዋቀረው አገዛዝ ስልጣንን ከተረከበ ጀምሮ በህዝባችን ላይ፣ በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ የግድያና የማፈናቀል እርምጃ ሲወሰድ ይህንን ዘግናኝ ድርጊት በመኮነን ማንነታቸውን አላስወቁም። ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መከበር ጠበቃ መሆናቸውን አላረጋገጡም። እንዲያውም ምንም ዐይነት ወንጀል እንዳልተፈጸመና እንደማይፈጸም ከአገዛዙ ጋር አብረው ሲቀመጡና ተጋብዘው ሲበሉ ይታያሉ። በህዝባችን ላይ የሚፈጸመውን ወንጀልና ዘግናኝ ድርጊት ለሰፊው ህዝብ በማሳወቅ ህዝቡ ወጣ ብሎ ድምጹን እንዲያሰማና ድርጊቱ እንዲቆም የሚወስዱት እርምጃ የለም። አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ነን ባዮች የድርጊቱ ተባባሪዎች ይመስል ዝም ብለው የሚመለከቱ ናቸው። ከአገዛዙ ጋር ውስጣዊ ስምምነት(Tacit Agreement) ያላቸው ይመስላል። ታዲህ በዚህ ዐይነት ቀውጢ ጊዜ ጩኸቱን ያላሰማ ፓርቲ በምን ተዓምር ነው በምርጫ ተወዳድሮ ቢያሸንፍ እንኳ ዐይነተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው? ባጭሩ ፓርቲዎች ለምሁራዊና ለሰብአዊ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለሚመሰረት ሰፋ ላለ ኢኮኖሚ እንቅፋት የሆኑ ናቸው ማለት ይቻላል። በአገራችን ምድር ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲደረግ ይህ ነገር መስተካከል አለበት፣ ወይንም እንደዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሰፋ ላለ ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል ለሀብት ፈጠራ የሚስማማ አይደለም ብለው መንግስትን ሲያፋጥጡ አይታይም።
ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት በአውሮፓ ምድር ፓርቲዎች ከመቋቋመቸው በፊት ከተማዎችና መንደሮች በደንብ ተገንብተዋል። ከተማዎችና መንደሮች በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች ተሳስረዋል። ሰፋ ያሉ ተቋማትና የባህልም ማዕከሎች ተገንብተዋል። ከረጅም ጊዜ የካፒታሊዝም ዕድገት በኋላ ፓርቲዎች ሲመሰረቱና ለምርጫም ሲወዳደሩ አዳዲስ ከተማዎችን የሚመሰርቱና ተቋማትን የሚገነቡ ሳይሆን ያለውን የሚያሻሽሉ ናቸው። በኢኮኖሚ ፖሊሲም እንደየ ኃይል አሰላለፋቸው የተለያየ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የውስጥ ገበያው እንዳይረበሽ የሚያደርጉ ናቸው። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ሁሉም ነገር ከዜሮ በመነሳት ነው መሰራትና መገንባት ያለበት። መንደሮችንና ከተማዎችን በአዲስ መልክና ሰው እንዲኖርባቸው አድርገን መገንባት አለብን። ግልጽነት ያለው የኢኮኖሚ አደራጃጀት ማዋቀር አለብን። የጥሬ-ሀብትንና የሰውን ጉልበት ለማንቀሳቀስና ተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ብቃቅትነት ያላቸው ተቋማት በየቦታው መገንባት አለብን። ለዚህ ደግሞ አዲስና ታግቶ የሚሰራ፣ ሞራላዊ ብቃትነት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ማሰልጠን ያስፈልጋል። በአጭሩ ተከታታይነት የሚኖረው ከአንድ ትውልድ ወደሚቀጥለው ሳይረበሽ የሚተላለፍ ስርዓት መመስረትና በየጊዜው ማሻሻል ያስፈልፍጋል። ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንነሳ ስልጣንን የጨበጠው ብልጽግና የሚባለውና ሌሎችም ብቃትም ሆነ ችሎታ ያላቸው አይመስሉም። ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ነው በብልጽግና ዘመን ያለውን፣ ያየነውንና ህዝባችንም የቀመሰውን የመረረ ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን መመርመር የምንችለው።

ዘመነ-ብልጽግና ወይም ዘመነ ሰቆቃ!

በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ ስልጣንን ከጨበጠ ከሶስት ዓመት በላይ አስቆጠረ። ዶ/ር አቢይ በመጀመሪያው አንድ ዓመት ህዝባችን በብዛት የሰጣቸውን ድጋፍ መሰረት በማድረግ ስርዓት ያለውና ህዝባችንን ለዕድገት በአንድነት የሚያነሳሳው የተቋም ማሻሻያና ሌሎች ስር-ነቀል እርምጃዎችን ሲወስዱ አልታዩም። ፓርኮችን ከመስራትና በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ እንደ ቴሌና አየር መንገድ የመሳሰሉትን በመንግስት ስር ያሉ የአገልግሎት ተቋማትን ለውጭ ኩባንያዎች በድርሻ ለመሸጥ ጉድ ጉድ ከማለት በሰተቀር ከህውሃት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመላቀቅ ሰፋ ያለ የስራ መስክ ሊከፍትና አገሪቱንም በጸና መሰረት ላይ እንድትገነባ የሚያደርግ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርጉ አይታይም። ይባስ ብለው አገራችንን በመዕለ-ነዋይ ስም ለአረቦችና ለተቀሩት የውጭ ባለሀብቶች ለመሸብሸብና የጨለማውን ዘመን ለማራዘም ደፋ ቀና ብለው ሲሰሩ ነው የምናየው።
ወደ መንግስት መኪናው ጋ ስንመጣም እስካሁን ድረስ ሳይታክቱ የሰሩት የአንድ ሰው አምባገነንነት እንዲነግስ ነው። በመሆኑም የህውሃት አገዛዝ በሌላ ዐይነት አገር አፍራሽና አፋኝ ስርዓት የተተካበትን ሁኔታ በግልጽ እንመለከታለን። መንግስታዊ አወቃቀሩ ወደ ፋሺሽታዊነት እየተለወጠና ህዝባችንም በፍርሃት የሚኖርበትን ሁኔታ እንያለን። በብልጽግና ስም የተደራጀው ፓርቲ ነኝ ባይና የመንግስቱ መኪና አንድ ላይ የተያያዙ እንጂ መንግስት የሚባለው የህዝብ አገልጋይ መኪና በአውቶኖመስ ደረጃ የሚንቀሳቀስና ኃላፊነቱን የሚወጣ አየደለም። የአገዛዙንም አወቃቀር ስንመለከት በኤክስኩቲቩ፣ በህግ አርቃቂውና በህግ አስፈጻሚው መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ ክፍፍል የለም። ፓርላሜንት የሚባለውም ምንም ሚና ስለሌለው ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሌክቸር የሚሰጡበት መድረክ ወደመሆን ደርሷል። በትክክል ለመናገር በአገራችን ምድር ዲስፖታዊ አገዛዝ ተመስርቷል ማለት ይቻላል። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን “ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” የሚለው አነጋገር ዛሬም የሚሰራበት ለመሆን በቅቷል። ለምሳሌ በአንድ የኢኮኖሚ ስብሰባ ላይ ተገኝተው አንዱ የዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ምሁር ስለቴሌ በድርሻ መልክ መሸጥ ጠቃሚ አይደለም፣ እንዲያውም ጎጂ ነው ብሎ ለማስረዳት ሲሞክር ለምንድነው እስቲ ዘርዘር አድርገህ አስረዳን ከማለት ይልቅ “ወስነናል” በማለት ነው በማስፈራራት መልስ የመለሱለት። ጠቅላይ ሚኒስተሩና የካቢኔት ሚኒስተሮች ሁሉንም ነገር በራሳቸው የሚወስኑና የኒዎ-ሊበራልን ፖሊሲ በሚያራምዱ በእርንስት ኤንድ ያንግ (Ernst and Young) በመሳሰሉት አገር አፍራሽ ድርጅቶች የሚመከሩ ናቸው። በኢኮኖሚክስና በፋይናንስ ሚኒስተር ውስጥ በሚኒስተር ዴኤታነት ተቀጥረው የሚሰሩት ተጠሪነታቸውና አገልጋይነታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ለዓለም ባንክ ነው።፡ ደሞዛቸውም በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ነው። ይህም ማለት እነዚህ ሰዎች በተጨባጭ ለውጭ ኃይሎች የሚሰሩ እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና የአገራችንን ኢኮኖሚ ሰፋ ባለ መሰረት ለማዋቀር አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስተሩና የካቤኔ ሚኒስተሮችም በህገ-መንግስቱ መሰረት በፓርሊያሜንቱ ፊት የማይጠየቁና በፓርሊሜንታሪ አጣሪ ኮሚቴም ስራቸው የሚመረመርና የሚጣራ አይደለም። ከዚህ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስተሩ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ አስተሳሰብ ባላቸው እንደነ አባዱላ፣ ሌንጮ ባቲና ሌሎች ፀረ-ዲሞክራቲክ ኃይሎች የሚመከሩ ናቸው። በዚህ መልክ በተዋቀረና በአድሃሪ ሰዎች ከተከበበ አገዛዝ ዲሞክራሲንና ፍትሃዊነት ያለውን አስተዳደር መጠበቅ በፍጹም አይቻልም። ወደሌሎች ጉዳዮችም ስንመጣ ፖሊሶች ለፍርድ ቤት የሚታዘዙ አይደሉም። ፍርድቤት አንድ እስረኛ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሲሰጥ ፖሊስ አልለቅም እያለ ግብግብ የሚፈጥርበትን ሁኔታ እንመለከታለን፤ እንሰማለንም። አንዳንድ አካባቢም፣ በተለይ በኦሮምያ ክልል ዳኞች በፖሊሶች እንደሚደበደቡ ይነገራል። ሰሞኑን እንደሰማነውና በቪዲዮም እንደተመለከትነው አንድ የአስራስምንት ዓመት ወጣት ወንጀል ሲሰራ ተገኝቷል በማለት በፖሊሶች ተደብድቦ በጥይት እንዲገደል ተደርጓል። ፖሊሶች በግልጽ ሰውን እንደዚህ በጠራራ ፀሃይ ላይ ሲደበድቡና ሲገድሉ የክልሉ መንግስት ዝም ብሎ ይመለከታል። የኦሮሞ ኮንግረስ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቻ ኢትዮ ኒውስ ለሚባለው ሚዲያ ላይ ቀርበው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ በኦሮምያና በሌሎች ክልሎች ከፍርድቤቶችና ከአቃቤ ህጎች ይልቅ ፖሊሶች የበለጠ ስልጣን ያላቸውና በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ለምን ፍርድ ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ነው በዝርዝር ያስረዱት። በእሳቸውም አባባል በደርግ የአገዛዝ ዘመን በቀይ ሽብር ወጣቱ በጠራራ ፀሀይ እንደሚገደል ሁሉ ዛሬም በተለይም በኦሮምያ ክፍል ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚፈጸም ተናግረዋል። ይህ ሁሉ ምንድነው የሚያረጋግጥልን? በዚህ ዐይነት ፈሺሽት መሰል አገዛዝ ሁኔታ ውስጥ የምርጫ ማድርገ ትርጉሙ ምን ላይ ነው?
ከዚህ ወጣ ብለን ስንሄድ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በቤናሽጉልና በምዕራብ ወለጋና ቀደም ብሎ በሻሸመኔ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሲካሄድና ሀብትም ሲወድም ዝም ብሎ የተመለከተ ነው። ሰሞኑን ደግሞ በካራቆሬ፣ በሸዋ ሮቢትና በአልጣዬ በተደራጀ መልክና በዘመናዊ መሳሪያ በመታጠቅ የብዙ መቶ ዓመታት ከተማዎች ሲወድሙና በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ መንግስት ዝም ብሎ የተመለከተ ነው። አንዳንድ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ራሱ በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ እጁ እንዳለበት ነው። ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልክ አንዳንድ ጄኔራሎች ለማስተባበል ሞክረዋል። እነዚህ ጄኔራሎች ከአማራ ልዩ ኃይልና ከፋኖዎች ጋር በመሆን በጦር ሜዳ ላይ ጥሩ ውጤት ቢያስመዘግቡም፣ በወለጋ፣ በመተክል፣ በሸዋ ሮቢት፣ በካራቆሬና በአጣዬ ላይ የደረሰውን ግፍ የመመልከት ኃይል አልነበራቸውም። ወይም ራሳቸው ተባባሪ ይመስል የተጠረጠረውን ጄኔራል ይህንን ሊያደርግ አይችልም ብለው ጠበቃ ሲቆሙ ታይቷል። ይሁ ሁሉ ነገር የሚያረጋግጠው እነዚህ ጄኔራሎችም ሆነ የመንግስትን መኪናን የሚቆጣጠረው አገዛዝ ሞራላዊና ምሁራዊ ብቃትነት እንደሌላቸው ነው። የተወሳሰበውን የህብረተሰባችንን አገነባብና ዛሬም አገራችን ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት በምሁራዊ መነጽር በመመልከት ጥበብ የተሞላበት ፖለቲካ ማካሄድ የማይችሉና አገራችንና ህዝባችንን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጡ ናቸው። በተለይም ሱዳን የፈጸመችውን ወረራና መሬት መያዝ አስመልክቶ የሚሰጡትን ገለጻና ዝም ብሎ መመልከት ስንከታተል የዶ/ር አቢይ አገዛዝና አንዳንድ ጄኔራሎች ለኢትዮጵያችን ሳይሆን ለሱዳን ጠበቃ የቆሙ ነው የሚያስመስለው። ነገሩን በጥብቅ ለተከታተለ ሱዳን ጦር ስትከፍትና መሬት ስትቆጣጠር ዝም ብሎ መመልከት የዶ/ር አቢይ አንደኛው ስትራቴጂ የአማራን ልዩ ኃይልና ህዝቡን ማዳከም ይመስላል። በአገዛዙ ዘንድ፣ በተለይም ደግሞ ኦሮሞ የበላይነትን መጎናጸፍ አለበት ብለው በሚያምኑት ዘንደ አማራ በሁሉም አኳያ መወጠርና መዳከም አለበት የሚል አስተሳሰብ የነገሰ ይመስላል።
ወደ ክልል አገዛዞች ስንመጣ አሮምያን አስተዳድራለሁ የሚለው አምባገነናዊ አገዛዝ እራሱን እንደ ነፃ መንግስት የሚመለከትና በሌሎች ክልሎች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ሰውን እስከመግደል ድረስ የሚደርስ ነው። በኦሮምያ ክልል ብቻ ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር እዚያው ተወልዶ ያደገ ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጣ የህብረተሰብ ክፍል አለ። ሌሎች ብሄረሰቦችም ይኖራሉ። እነዚህ ሁሉ በሚኖሩበት አካባቢ እንደሁለተኛ ዜጋ የሚታዩና መጤ እየተባሉ የሚንገላቱና የሚፍናቀሉና በፍርሃትም የሚኖሩ ናቸው። በመሰረቱ ዛሬ ኦሮምያ ተብሎ የተካለለው ቦታ ኦሮሞዎች የሚኖሩበት አልነበረም። በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ኦሮሞዎች በተስፋፊነት የያዟቸው ቦታዎች ናቸው። ኦሮሞዎች ከመስፋፋታቸው በፊት በ14ኛውና በ15ኛው ክፍለ-ዘመን በተለይም ከአማራው ክፍል ሃይማኖትን ለማስፋፋት ተብሎ ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች እየተሰማሩ ያስተምሩና አካባቢውን ያለሙ እንደነበር የታወቀ ጉዳይ ነበር። እዚያም ተዋልደው ለብዙ መቶ ዓመታት ከትውልድ ትውልድ እየተራቡ የመጡ ናቸው። አብዛኛዎቹ በደቡቡ ክፍል የነበሩ አገዛዞችም ለክርስቲያኑ አገዛዝ ግብር የሚከፍሉ ነበሩ። ይህ ሁሉ ነገር በግልጽ በማስረጃ መልክ ተጽፎ እያለና አፄ ምኒልክም ግዛታቸውን ዘመናዊ ለማድረግ የጥገና ለውጦች ያደረጉትን እንደወንጀል ተቆጥሮ በትረካ ላይ በመመስርት በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ እንደዚህ ዐይነት አሰቃቂ እርምጃ መውሰድ አሁን ባለንበት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘመን መደረግ የነበረበት ተግባር አልነበረም። የሚያሳዝነው ነገር ግን በኢትዮጵያ ምድር ተወልደውና አድገው፣ ትምህርትቤት ሄደውና በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ተምረውና ተመርቀው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት የድሮዎችን አገዛዝና ህዝባችንን ከማመስገን ይልቅ ያስተማራቸውን ህዝብ ሲገድሉና ሲያባርሩ ስናይ ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ አላቸው ወይ? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። መማረርና መቆጨት የነበረበት ደሃው ገበሬ ነበር። ይሁንና እነዚህ ተንደላቀው ያደጉ በአጉል ትረካ ጭንቅላታቸው ስለተቀረጸ ኢትዮጵያን እንዳለች መበወዙን ተያይዘውታል። ማንኛውም ነገር ከእኛ ፈቃድ ውጭ መደረግ አይችልም በማለት ሁሉንም ነገር ወደ መቆጣጠር አምርተዋል።
ያም ሆነ ይህ በብልጽግና የአገዛዝ ዘመን አገራችንና ህዝባችን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። ህዝባቸን በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ወድቋል። ጠዋት ወጥቶ ማታ ተመልሶ ቤቱ ለመግባቱ እርግጠኛ አይደለም። በተለይም ዲሞግራፊውን መለወጥ ያስፈልጋል በሚል ስም በአላዋቂዎች አዲስ አበባ ውስጥ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከባላገር አምጥቶ ማስፈር ከተማይቱን የኪስ አውላቂዎች፣ የማጅራት መቺዎችና የገዳዮች መናኸሪያ አድርጓቷል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ እነ ሺመልስ አብዲሳ የዛቱት ነገር ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው። ይኸውም አዲስ አበባን ትርጉም እንዳይኖራት ማድረግ። የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውና ከጄኔባ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የምትቆጠረው አዲስ አበባ ትርጉሟን የምታጣበት ጊዜና፣ እነዚህ ተቋማትና የአፍሪካ አንድነት መቀመጫቸውን ወደሌላ የአፍሪካ አገር የሚያዛውሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ማለት ነው። ዶ/ር አቢይና የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪዎች ይህንን ዕውን ለማድረግ ሌት ተቀን የሚሰሩ ነው የሚመስለው።
ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ በዛሬው ወቅት ምርጫ ማካሄድና በምርጫ መሳተፍ፣ እንዲሁም ለምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ላለው አሰቃቂና አገርን አፍራሽ አካሄድ ዕውቅናን እንደመስጠት ይቆጠራል። ምርጫው ቢካሄድ በእርግጥ “በአሸናፊነት” ሊወጣ የሚችለው ብልጽግና የሚባለው ሞራላዊና ምሁራዊ ብቃት የሌለው ፓርቲ ነኝ ባይ ነው። እደምናየው አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ቢሮዎች የሏቸውም፤ በየቦታው እየሄዱም ቅስቀሳ ለማድረግ አይችሉም። ይህም ማለት ምርጫው በሰላምና በግልጽነት የሚካሄድ አይሆንም ማለት ነው። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ አሸናፊ ነኝ ብሎ የሚወጣው ብልጽግና የሚባለው የጨለማውንና የሰቆቃውን ዘመን የሚያራዝመው የዶ/ር አቢይ ፓርቲ ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም በዚህ ዐይነት ግልጽነት በሌለበት፣ ሰላም ባልሰፈነበት፣ ግድያና መፈናቀል በተስፋፋበት አገር ውስጥ ምርጫ ማካሄድ በታሪክና በህዝብ ላይ እንደ መቀለድ ይቆጠራል። በሌላ ወገን ደግሞ ራሱ የብልጽግና ፓርቲ ነኝ የሚለው ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ስምንት ፖሊሲ ነክ በሆኑ ነገሮች፣ ማለትም በስራ-አጥነት፣ በኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ በመንግስት ሚና፣ በብሄራዊ ደህንነትና በሰላም ጉዳይ ላይ፣ በትምህርት ፖሊሲ ላይ፣ በማህበራዊ ፖሊሲና በህገ-መንግስቱ…ወዘተ. … ወዘተ. ላይ ጊዜ የለኝም በማለት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመከራከር ፈቃደኛ እንዳይደለ አስታውቋል። በተለይም አቶ ዛዴግ አብርሃ የብልጽግና አመራር አካል የሆኑት ግልጽ በሆኑ ፖሊሲ ነክ ጉዳዮች ላይ በሰው ፊት ቀርቤ ለመከራከር ፈቃደኛ አይደለሁም በማለት በግልጽ ተናግረዋል። በሌላ ወገን ግን የብልጽግና ፓርቲ በየቦታው እየተዘዋወረ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርግ ይታያል። ይሁንና ግን አብዛኛው ህዝብ ማንበብና መጻፍ በማይችልበት አገርና የየፓርቲዎችን ፕሮግራምና ፖሊሲዎችን አንብቦና ተረድቶ የራሱን አስተያየትና ፍርድ ለመስጠት በማይችልበት አገር የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል እንደመስራት የሚቆጠር ነው።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም እዚህ አውሮፓና አሜሪካ እየኖሩ ምርጫ መካሄድ የለበትም ብለው የሚጽፉትን የሚሳደቡ አንዳንድ ምሁራን ነን ባዮች ያሉበትን ቦታ የማያውቁና በ21ኛው ክፍለ-ዘመንም እንደሚኖሩ ያልተገነዘቡ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በዶ/ር አቢይ ፍቅር ያበዱ ይመስላሉ። የሰውየው ስም ሲነሳ ያንቀጠቅጣቸዋል። ፍቅራቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሳይሆን ከአንድ ሰው ጋር ነው። ዋና አለማቸውም አዲስና ያደገች፣ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊት አገርን ማየት ሳይሆን ለማኝንና የምትበታተንን አገር ነው። ይህንን ጉዳይ አውጥተው ባይናገሩም ተጨባጩን የአገራችንን ሁኔታ ለማየት አለመቻላቸውና በአንድ ግለሰብ ፍቅር መታወራቸው እንደዚህ ብሎ ከመደምደም በስተቀር ሌላ ነገር ማለት አይቻልም። ስለሆነም በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ በአገራችን ምድር ዲሞክራሲ እንዳያብብ፣ ዘመናዊ ተቋማት እንዳይገነቡ፣ ሰፊውን ህዝብ ከድህነትና ከለማኝነት የሚያላቅቀው ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን፣ የኢኮኖሚው መሰረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዳይሆን ማድረግ፣ ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችና ለሰፊው ህዝብ የሚሆን ከአገራችን የአየር ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ቤቶች እንዳይሰሩ፣ ባጭሩ በአገራችን ምድር ሰፊው ህዝብ ማንነቱን እንዲገነዘብና በአዲስ መንፈስ በመነሳሳት አገሩን በአዲስና በጸና መሰረት ላይ እንዳይገነባ መሰናክል እንደመፍጠር ይቆጠራል። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com

Bekele, Fekadu; African Predicaments and the Method of Solving them
effectively, Berlin, 2016