The New Ruling Elite in Ethiopia that destroys its country
ደሞዝ እየተከፈላቸውና እየተቀለቡ አገር የሚያፈራርሱና ማንነትን ተኮር
ያደረገ ጭፍጨፋ የሚፈጽሙ፣ እንዲሁም ህዝብን የሚያፈናቅሉ
አዲሶቹ የአገራችን ገዢዎች!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ጥር 19፣ 2023
መግቢያ
እንደሚታወቀው ማንኛውም ግለሰብ አንድ መስሪያ ቤት ወይም ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ በሚሰራበት ጊዜ በስራ ቦታው ብቃትነትን ማሳየትና ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን በሚሰራበት መስሪያ ቤት ወይም ኩባንያ ውስጥ ታማኝነት የሚጣልበትና ከመሰል የስራ ባልደረቦቹ ጋር በፀባይ የሚግባባ መሆን አለበት። የአንድ መስሪያ ቤት ብቃትነትና ለህዝብ የሚሰጠው አገልግሎት የሚመዘነው ወይም የአንድ ኩባንያ ምርታማነትና ምርቱ በገበያ ላይ ተቀባይነት ማግኘት በመስሪያ ቤቱ ወይም በኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው በሚሰሩት ሰራተኞች ብቃትነትና ኃላፊነትን መወጣት ነው። በተለይም ደግሞ አንድ አምራች ኩባንያ፣ ለምሳሌ መኪናን እያመረተ ለገበያ የሚያቀርብ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጣለው በማኔጅሜንቱና ማኔጅሜንቱን በሚመራው ኃላፊ ሰው ነው። ስለሆነም ማኔጅሜንቱም ሆነ፣ ሌሎች ኢንጀነሮችና እስከተራ ሰራተኛ ድረስ በተመደቡበት ኃላፊነት ብቃትነታቸውን የሚያሳዩ ከሆነ ኩባንያው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ በመሆን በየጊዜው አዳዲስና የተሻሻሉ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ቀስ በቀስም ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የመያዝ ዕድል ያጋጥመዋል። በተለይም በማኔጅሜንት ውስጥ ጊዜውን የጠበቀ መሻሻል ካልተደረገ ወይም ኃላፊነት የተሰጠው ሰው በሙስና ውስጥ ከዘፈቀ፣ ወይም ደግሞ መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ከዋጋ አንፃር በማየት ርካሽ የመለዋወጫ ዕቃ ካስገባ ወይም ደግሞ ሶፍትዌሩን ማኑፕሌት ካደረገና ከተነቃበት ኩባንያው በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ቅጣት ሲከፍል፣ የማኔጅሜንቱ ኃላፊ ደግሞ ከስራው ቦታ ይነሳል። እንደገና የመቀጠር ዕድልም አያገኝም።
ወደሌሎች ነገሮችም፣ ለምሳሌ ከፍተኛ ኃላፊነትን ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ጽናትን የሚጠይቁ ለምሳሌ እንደፓይለት የመሳሰሉ ሙያዎች፣ ማንኛውም ዐይነት የምህንድስና ስራና ዕውቀት፣ አውሮፕላንና መኪናን መስራት የመሳሰሉት በቀጥታ የሚያያዙት ከሰው ህይወት ጋር ስለሆነ ፓይለቶችም ሆነ መሀንዲሶች ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ናቸው። ተሳፋሪውም ሆነ አዲስ መኪና ገዝቶ ለመንዳት የሚፈልግ ሰው ዕምነቱን የሚጥለው በፓይለቶችና መኪናን በሚሰሩት በመሀንዲሶች ላይ ነው። ይህ ዐይነቱ የአሰራር ልምድና ዕምነትን በሰራተኞች ላይ መጣል በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የተስፋፋና ሙሉ በሙሉ ተቀባይነትን ያገኘ ነው። የምንበላቸው ምግቦችና የምንጠቀምባቸው ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በሙሉ በሰው ህይወት ላይ ጉዳትን እንዳያደርሱ ወይም ጤንነትን እንዳያቃውሱ ሆነው መሰራት አለባቸው። ማንኛውም ነገር፣ በተለይም መኪናም ሆነ ሌሎች የኤሊክትሮኒክስ ዕቃዎችና ማቴሪያሎች ፈተናንና ሙከራን ካለፉ በኋላ ነው ገበያ ላይ የሚቀርቡት። ወዲያውኑ ተመርተው ወዲያውኑ የሚሸጡ አይደሉም ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ኩባንያ በተከታታይ በሰው ህይወት ላይ አደጋን የሚያስከትል ምርት በሚሸጥበት ጊዜ ፈቃዱን ይነጠቃል።
ወደ መንግስት መስሪያቤትም ስንመጣ፣ ምርጫን አሸንፎ ስልጣን ላይ የሚወጣ ፓርቲ ስልጣኑን ከመረከቡ በፊት ከጠቅላይ ምኒስተሩ ጀምሮ ሌሎች ምኒስተሮችም ፓርሊያሜንት ውስጥ የፓርሊያሜንት ፕሬዚደንቱ ፊት በመቆም ህገ-መንግስቱን አስመልክተው ቃለ-መሃላ የመፈጸም ግዴታ አለባቸው። ሲምሉም በህገ-መንግስቱ መሰረት በህዝብ ላይ ሊክሰት የሚችለውን አደጋ በሙሉ እከላከላለሁ፤ የህዝቤንም ጥቅም አስጠብቃለሁ በማለት የጠቅላላው ህዝብ ጠበቃ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ ማለት ነው። ስለሆነም አንድ ጠቅላይ ምኒስተር ጠቅላይ ምኒስተር ስለሆነ እንደፈለገው ሁሉን ነገር የማድረግ ልዩ መብት የለውም። ማንኛውም አገርንና ህዝብን የሚመለከት ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት መመርመርና መጠናት አለበት። ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜም ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምም ሆነ ጉዳት በፓርሊያሜንት ውስጥም ሆነ በሲቪል ሶሳይቲው ዘንድ ሰፊና የጠለቀ ውይይትና ክርክር መካሄድ አለበት። በተጨማሪም የተለያየ ሙያ ባላቸው ኤክስፐርቶች መገምገም አለበት። ይህም ማለት አንድ ጠቅላይ ምኒስተር ምኒስተሮችን የመጠባበቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጠቅላይ ምኒስተሩም ሆነ እያንዳንዱ ምኒስተር ስራቸውን ለፓርሊያሜንቱ ማቅረብና መገምገም አለባቸው። እያንዳንዱም ፓርሊሜንቴሪያን በሚሰጠው የሰዓት ገደብ ውስጥ በአገዛዙ የሚቀርበውን ሪፓርት የመተቸትም ሆነ በምክንያታዊ መንገድ የመደገፍ መብት አለው። ከዚህ ውጭ እያንዳንዱ ምኒስተርም ሆነ ራሱ ጠቅላይ ምኒስተሩ ከህገ-መንግስቱ ውጭ ኃላፊነት የጎደለው ስራ ሲሰሩ በፓርሊያሜንት አጣሪ ኮሚቴ የመመርመርና የመገምገም ግዲታ አለባቸው። ድርጊታቸው አደገኛ ከሆነና አገርንና ህዝብን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከሆነ በዕምነት ድምጽ ማጣት ከገዢነታቸው እንዲወገዱ ይደረጋሉ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ድርጊትና ወንጀል እየፈጸሙና እየተሳሳቁ ስልጣን ላይ የመቆየት መብት የላቸውም ማለት ነው። በመጥፎ ድርጊታቸውም በህግ ፊት እንደማንኛውም ወንጀለኛ መከሰስ አለባቸው። ስልጣንን ስለያዝን የፈለግነውን ነገር ማድረግ ስለምንችል በህግ የመጠየቅ ግዴታ የለብንም ሊሉ አይችሉም። በተለይም በተደራጀ መልክና በዕውቅ በዓለም አቀፍ የአገዛዝ ሰንሰለት ውስጥ በመግባትና የተሰጣቸውን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ አገዛዞች የአገርን ጥቅም፣ ታሪክንና ብሄራዊ ነፃነትን ያጎደፉ ድርጊቶችን ከፈጸሙ በህግ ፊት መቅረብና መጠየቅ፣ እንዲሁም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። ወንጀል እየሰሩ፣ ህዝብን እያሰገደሉ፣ ወይም አንድ ብሄረሰብ በማንነቱ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል የማይመለከታቸው ከሆነና ዝም ብለውም የሚታለፉ ከሆነ እነሱን የሚተካው ሌላ ኃይል ተመሳሳይ ወንጀል እየሰራ የሚታለፍ ይሆናል። እንደልምድም ስለሚወሰድ በዚህ መልክ አንድ ህዝብና አገር ይበደላሉ። ስለሆነም ማንም ይፈጽመው ወንጀል ስለሆነ ወንጀለኛው የግዴታ መጠየቅና መቀጣት አለበት።
ወደ አገራችን ስንመጣ ግን የገዢው መደብ ኃላፊነት፣ ከጠቅላይ ምኒስተሩ ጀምሮ እስከሌሎች ምኒስተሮች ድረስ ያለው ተግባርና ኃላፊነት በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም አገርንና ህዝብን የሚጎዳ፣ ብሄራዊ ነፃነትን የሚያስደፍር እርምጃ ሲወስዱ፣ ማህበራዊ መዝረክረክ ሲፈጠር ዝም ሲሉ፣ በተለይም በተሳሳተ ወይም በኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሲፈጠር … ወዘተ. ወዘተ. ማንም የሚጠይቃቸው የለም። ችግሮቹ እየተወሳሰቡና በቀላሉ መቀረፍ የማይችሉ ስለሚሆኑ ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አንፃር ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚያናጋ ሁኔታ በመፈጠር በቀላሉ ሊገታ የማይችል የፖለቲካ ቀውስ ሊከስት ይችላል። በተለይም አሁን በግልጽ እንደሚታየው የአገራችን ጠቅላይ ምኒስተር ፍጹም አምባገነን በመሆንና ልጠየቅም አልችልም በማለት ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ እስከ ባህላዊ፣ ከሚሊታሪ ቀውስና እስከ ብሄራዊ ነፃነት መደፈር ድረስ የሚያስከትል ወንጀል እየሰራ ማንም ሊነካኝና ሊሟግተኝ አይችልም በማለት ሰፊው ህዝባችን ግራ ተጋብቶ እንዲኖር ለማድረግ በቅቷል። ከዚህም በላይ በመሄድ በተጨባጭ አገርን የማፈራረስ ተግባር የሚፈጽምና፣ በተለይም ማንነትን ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋና ማፈናቀል እንዲካሄድ የሚተባበርና ዝም ብሎ የሚያይ ጠቅላይ ምኒስተር ነው በዛሬው ወቅት አገራችንን አስተዳድራለሁ የሚለው። ጠቅላይ ምኒስተሩ ፍጹም አምባገነን ከመሆኑ የተነሳ ሊጠይቁት ወይም ሊሟግቱት የሚፈልጉትን ሁሉ በዚህም በዚያም ብሎ አይ ያስራቸዋል፣ ካሊያም ደግሞ በአንዳች መንገድ ደብዛቸው እንዲጠፋ ያደርጋል። በመንግስት ተቋማትም ሆነ በአገዛዙ ላይ ትችትን ማቅረብ እንደወንጀል በመቆጠር ተቺዎች ትችታቸው ተገቢና የሚያሳምን ቢሆንም ካለበቂ ምክንያት በወታደሩ ላይ የመተቸት መብት የለባችሁም በማለት ይታሰራሉ። እንግዲህ ይህ ዐይነት የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነትና ህገ-መንግስቱን የሚፃረር ስራ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው የሚፈጸመው። የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታም ስንመለከት ሁሉ ነገር የተመሰቃቀለና፣ ልክ የማዕክለኛው ክፍለ-ዘመን ውስጥ የምንገኝ ይመስል አንድ ግለሰብ እንደፈለገው የሚጋልብባት አገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የመንግስትና የአንድ አገዛዝስ ዋናው ሚና ምንድነው? አንድ አገዛዝስ እንደፈለገው አንድን አገር የማመሰቃቀል፣ ሀብቷን የመዝረፍ፣ በህዝብ ላይ ማንነትን ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋ ሲካሄድ ዝም ብሎ የመመልከት፣ ወይም አያገባኝም የማለት መብት አለው ወይ? እንደዚህ ዐይነት ገደቡን የሳተ አገዛዝስ ስልጣን ላይ የመቆየት መብት አለው ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች አጠር መጠን ባለ መልክ እንመርምር;
የመንግስትን ምንነትና አወቃቀር የመረዳት ችግር!
በአብዛኛዎቻችን በተለይም በፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ በዚህም በዚያም ድምጻችንን በምናሰማው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር መንግስት ማለት ምን ማለት እንደሆነና፣ ተግባሩስ ምን እንደሆነ በቅጡ አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ በህዝብ ተመረጠም አልተመረጠም መንግስት የሚባለው አንድ የገዢ መደብ የሚቆጣጠረው መኪና የታሪክ ግዴታ የሆነውን ያህል፣ የግዴታ በጊዜው መታደስና መሻሻል፣ እንዲሁም ከሁኔታዎች ጋር እንዲስማማ ሆኖ መዋቀር እንዳለበት አለመረዳት ነው። ያለፉትን ከሃምሳ ዓመታት በላይ የበለጠ የፖለቲካ ትግል በጥብቅ ለተከታተለ መንግስትን አስታኮ የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናትና ትንተና ለመደረግ ባለመቻሉ መንግስትንና የገዢ መደቦችን አስመልክቶ በመሀከላችን ግልጽ የሆነ አስተያየት በፍጹም የለም። ስለሆነም መንግስትን ፍጹማዊ እንደሆነና፣ እንደፈለገው ሁሉን ነገር ሊያደርግ እንደሚችል በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ አስተሳሰብ ሆኗል። ከዚህም በመነሳት የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠር ሁሉ የሚፈራ፣ ካለአግባብ የሚከበርና ከህግና ከህዝብ በላይ እንደሆነ ተቀባይነትን ያገኘ ግንዛቤ ለመሆን በቅቷል።፡ ስለሆነም ማንኛውም እየተነሳ ካለብዙ መጨነቅ፣ ማውጣትና ማውረድ በድፍኑ መንግስት መንግስት ይድረስልን እያለ ይጮሀል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ይድረስልን የሚባለው መንግስት ለምን ራሱ ጨፍጫፊና አስጨፍጫፊ እንደሆነ፣ ወይም ደግሞ ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ማፈናቀል ሲካሄድ ለምንድነው ዝም ብሎ የሚመለከተው? ተብሎ ጥያቄ አይቀርብም።
የመንግስትንና የአገዛዞችን ተግባር ውስጣዊ ይዘት በሚመለከት ከፕሌቶ ጀምሮ እስከ ሊበራሎችና የማርክሲስት ቲዎሬቲሺያን ድረስ ግልጽ የሆነ አቋምና የቲዎሪ ጥናት አለ። ፕሌቶና የፕሌቶንን ፈለግ የሚከተሉ ምሁራን በአንድ አገር ውስጥ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠር አገዛዝ የግዴታ ህዝቡን ፍትሃዊ በሆነ መልክ ማስተዳደር እንዳለበት ያስተምራሉ። በተጨማሪም መንግስትን የሚቆጣጠር የገዢ መደብ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ብቃትና የፍልስፍና ዕውቀት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በፍልስፍና መነፅር ብቻ ነው የተወሳሰቡና የተሳሰሩ ነገሮችን መመልከትና ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ሳይንሳዊ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ከሰማይ ዱብ የሚሉ ሳይሆኑ ስልጣንን የሚይዙ ኃይሎች በቂ ዕቅወትና ሳይንሳዊ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በጭፍንና በራሳቸው ስሜት በመገፋት ህብረተሰቡን የሚጎዱ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ ነው። በእነሱ ዕምነትም በመንግስትና በአገዛዙ በሚሰሩ ስህተቶች ወይም ኢ-ፍትሃዊነት የተሞላበት አገዛዝ የተነሳ አንድ አገርና ህዝብ አንድ ላይ በመተሳሰርና በመተጋገዝ እንደሰውና እንደህዝብ ተግባራዊ ማድረግ የሚገባቸውን ነገሮች እንዳያደርጉ ይገደዳሉ። ስለሆነም ኢ-ፍትሃዊነት በሰፈነበት አገር ውስጥ ህዝባዊ ስምምነት ሊኖር አይችልም። የተሟላ ዕድገትንና ነፃነትም ሊኖር አይችልም ይላሉ። በሶክራተስ ተመስሎ አያሌ ጽሁፎችን በጻፈው በፕሌቶ ዕምነት የአንድ አገር መሪና በሱ ዙሩያ የሚሰበሰቡ ግለሰቦች አይ ፈላስፋዎች መሆን አለባቸው፤ አሊያም ደግሞ በፈላስፋዎችች የሚመከሩና የሚመሩ መሆን አለባቸው ይላል።
ይሁንና እነፕሌቶን ይህንን አስተሳሰብ ያፈለቁት እንደዛሬው ዘመን መንግስት የሚባለው ነገር በተለያዩ ተቁማት ባልተዋቀረበትና፣ የካፒታሊዝም ስርዓት ባልሰፈነበት ዘመን ነበር። በጊዜው በእነሱ ዘመን ብዙ ነገሮች ያልተወሳሰቡ ስለነበሩ፣ መንግስት የሚባለው ነገር በወታደር፣ በፀጥታ ኃይል፣ በስለላ ድርጅት፣ በፖሊስ፣ በፍርድቤትና በልዩ ልዩ ተቋማት የሚገለጽ አልነበረም። ስለሆነም ጭቆናውና በግለሰቦች ላይ ያለው ተፅዕኖ ዛሬ እንደምናየውና፣ በተለይም በአገራችን ምድር ጎልቶ እንደሚታየው መጠኑን የሳተ ጭፍጨፋና ማፈናቀል አይካሄድም ነበር ማለት ይቻላል። ወደ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያም በኋላ እስከ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ በአብዛኛዎች የአውሮፓው አገሮች ግለሰብአዊ ነፃነትን ያፈኑ አስቸጋሪ ወም ዲስፖታዊ አገዛዞች ስለነበሩ በጊዜው የነበሩት ፈላስፋዎች፣ ሊበራል በመባል የሚታወቁ የተገለጸላቸው ምሁራን ሁኔታው ስላስገደዳቸው የግዴታ አንድ አገዛዝ ገደብ እንዲኖረው ራሱ በህግ የሚገዛና የህግ የበላይነትን የሚያከብር መሆን እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። በተለይም በጊዜው ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው የከበርቴው መደብና እየዳበረ የመጣው የስራ ክፍፍል ዲስፖታዊ አገዛዞች በሰፈነቡት አገር ውስጥ ሊስፋፋና ሊዳብር አልቻለም፤ ስለሆነም የግዴታ የሪፑብሊካን አስተሳሰብ ተግባራዊ መሆንና የግለሰብአዊ ነፃነት መከበር እንዳለበት የተረዱ ከፍተኛና የተወሳሰበ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ለከበርቴው መድብና ለአገዛዞች የቲዎሪ መሰረት በመዘርጋት የግዴታ ጥገናዊ ለውጥ እንዲካሄድ ተፅዕኖ ማሳደር ተቻለ። ከተማዎችና መንደሮች ሲገነቡና የስራ-ክፍፍል ሲዳብርና የንግድ ልውውጥ ሲካሄድ ዲስፖታዊ አገዛዞች በዚህ ዐይነቱ እያደገና እየተስፋፋ በመጣ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ቀስ በቀስ ሊዳከሙ ቻሉ። ይሁንና ግን በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የፈለቀው የሊበራሊዝም ቲዎሪና የህግ የበላይነት አስተሳሰብ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ካፒታሊዝም እያደገና እየተወሳሰበ ከመጣ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጊዜ ጀምሮ በተለይም በካፒታሊዝም ዕድገትና ውስብስብነት የተነሳ በወዝአደሩ ላይ የሚደረገው ብዝበዛና ጭነት በማየሉ በጊዜው የነበሩት የማርክሲስት ቲዎሬቲሽያን ይህ ዐይነቱ የመንግስት አወቃቀር የመጨረሻው ሳይሆን፣ የግዴታ የገዢው መደብ መሳሪያ በመሆን ጭቆናን በተወሳሰበ መልክ የሚያስፋፋ እንደመሆኑ መጠን ይበልጥ ዲሞክራሲያዊና ሶሻሊስታዊ የሆነ መንግስታዊ አወቃቀር መመስረት እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። በካፒታሊዝም ስርዓት ላይ የተመሰረተው የመንግስት አወቃቀር የግዴታ የኢኮኖሚው መሰረት ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ ይህ ዐይነቱ መንግስት ህዝባዊ ባህርይ የሌለውና በተለያዩ የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ሀብት ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ካፒታሊስቱ መደብ የሚያስተላልፍ ስለሆነ በተለይም የሰራተኛው መደብ እንደልፋቱ ማግኘት የሚገባውን ለዩ ልዩ አገልግሎቶች ማግኘት አይችልም ነበር። በሚያገኘውም ተጨባጭ ደሞዝ ብቻ ከተወሰኑ ነገሮች ባሻገር ለጤንነቱ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ሊሸፍንለት አይችልም ነበር። በካፒታሊዝም ዕድገት የተነሳ የመንግስት ጥያቄ ያለቀለቀት ጉዳይ ስለሆነ የመሻሻል ጥያቄዎች መነሳት የለባቸውም በሚል እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አልተቻለም።
ይህ የሚያሳየን ምንድነው? መንግስት የሚባለው መኪናና የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠሩት ገዢዎች የመደብ ባህርይ እንዳላቸውና ሳይወዱ በግድ ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያደሉ ነው። ይሁንና በጊዜው እያየለ የመጣው የሰራተኛው መደብ እንቅስቃሴና የሱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ፓርቲዎች መፈጠራቸው የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው እንደፈለገው በጭፍን ወደፊት የሚገፋ ሳይሆን የግዴታ የጥገና ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ተረዳ። ካለበለዚያ ተከታታይነት ያለው ህብረተሰብአዊ ግጭት ስለሚፈጠር የወዝአደሩ መደብ በሙያ በመደራጀትና ተጠሪዎችን በመምረጥ ከአሰሪዎች ወይም ከካፒታሊስቶች ጋር የሚደራደርበት አመቺ ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ስለሆነም በፋብሪካ ውስጥ ተቀጠሮ የሚሰራው ሰራተኛ የስራ ሰዓት ገደብ፣ ከዚያም በማለፍ ከስራው ቦታ በሚባረርበት ጊዜ ሊኖረው የሚችለው መብት በህግ መደንገግ ቻለ። ከዚህም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሰራተኛው ከስራ-መስኩ በሚባረርበት ጊዜ ሌላ ስራ እስኪያገኝ ድረስ የስራ-አጥ አበል ማግኘት እንዳለበት በማመንና፣ ማህበራዊ የጥገና ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው በመረዳት ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ጭቆናዊ ከሆነው አሰራሩ በመጠኑም ቢሆን በመላቀቅ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ አነሰም በዛም ግለሰብአዊ ነፃነት የሚጠበቅበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ።
በዚህ መልክ አጠር መጠን ብሎ የቀረበው የመንግስት አወቃቀርና የገዢ መደቦች ባህርይና የአገዛዝ ስልት የሚያረጋግጠው የመንግስት መኪናና የገዢ መደቦች አገርን በህግ የማስተዳደር ኃላፊነትን መረዳት ግዴታ የትግል ውጤት እንደሆነ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩት የዲሞክራሲን ጥያቄ፣ ግለሰብአዊ ነፃነትንና የህግ የበላይነትን ማመንና በዲሞክራሲያዊ መርሆች መገዛት ፈቅደው የተቀበሉት ሳይሆን በትግል የተገኘና በከፍተኛ ደረጃ የተገለጸላቸው ምሁራን የማያቋርጥ ትግል ስላደረጉና ህብረተሰብአዊ አስተላለፉም ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ ነው። የተገለጸላቸው ምሁራንና የወዝአደሩ ተጠሪዎች ሳይፈሩ ሳይቸሩ የመንግስትን መኪና ከጨበጠው የገዢ መደብና ከከበርቴው መደብ ጋር በመጋፈጣቸው ገዢዎችንና የከበርቴውን መደብ ጭንቅላት መግራት ቻሉ። የገዢውና የከበርቴው መደብ እንደፈለጋቸው ሊፈነጩ እንደማይችሉና አንድን ህብረተሰብ በአቦሰጡኝና በማንአለኝበት ማስተዳደር እንደማይችሉ በመገንዝባቸው ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኘነት የህግ የበላይነትና ግለሰብአዊ ነፃነት የሚጠበቁበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። በተለይም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕምርታን ማግኘትና፣ የማኑፋክቸሪንግ መስፋፋት የመንግስቱ መኪና ከዚህ ዐይነቱ ውስጣዊ-ኃይል ካለው የካፒታሊስት የአመራረት ስልት ጋር የግዴታ እንዲጓዝ አደረገው። በተለያዩም የመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች የካፒታሊዝምን ዕድገት የሚያደናቅፉና በሙስና የተተበተቡ ሳይሆን የግዴታ በቂ ስልጠና የሚሰጣቸው በመሆን ለአጠቃላዩ የህብረተሰብ ዕድገት አመቺ ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ።
እንደ ኢትዮጵያ ባለው፣ በብዙ ሁኔታዎች ወደ ኋላ በቀረ አገር ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የመንግስት መኪና አወቃቀር የካፒታሊስት አገሮች የተጓዙበትን ሂደት ለመጓዝ ባለመቻሉና በየጊዜው በምሁራን እየተገመገመ እንዲሻሻል አለመደረጉ ነው። ቢያንስ ከአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ የተዋቀረውን ቢሮክራሲያዊ የመንግስት መኪና በምንመረምርበት ጊዜ ከውስጥ ቀስ በቀስ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ እየተኮተኮተና እየዳበረ ለመምጣት ባለመቻሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና ግለሰብአዊ ነፃነትን የማፈን ኃይሉ ከፍተኛ ነበር ማለት ይችላል፤ አሁንም ነው። በንጉሳዊ አገዛዝ ዙሪያ የተሰባሰቡት በገዢው መደብ ውስጥ የተካተቱት፣ በተለይም የምኒስተርነትን ማዕረግ የተከናነቡት ዘመናዊ የሚባለውን ትምህርት የቀሰሙ ቢሆንም ለአንድ አገር የተሟላ ዕድገት የሚያመች ዕውቀት የሌላቸውና፣ የነፃነትንና የዲሞክራሲን ትርጉም የተረዱ ባለመሆናቸው ከውስጥ መደረግ ያለበትን መንግስታዊ የጥገና ለውጥ ማድረግ ተሳናቸው። በተለይም ውስን በሆነው ምሁራዊ ሁኔታ የተነሳ ከካፒታሊዝም ዕድገት አንፃር፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂዎች መዳበርና እየተወሳሰበ የመጣውን የህብረተስብ ችግር ለመፍታት ሲባል የመንግስቱ መኪና መሻሻልና መስፋፋት እንዳለበት የሚያስተምርና ግፊት የሚያደርግ የተገለጸለት ኃይል ባለመኖሩ የመንግስቱ መኪና ከጭቆናዊ ባህርይው ሊላቀቅ አልቻለም። ይሁንና የአፄ ኃይለስላሴን አገዛዝና የመንግስትን መኪና በምንመለከትበት ጊዜ ከዚያ በኋላ ብቅ እንዳሉት አገዛዞች፣ ከደርግ ጀምሮ እስከወያኔና እስከዛሬው አገዛዝ ድረስ ይህን ያህልም ጨቋኝ እንዳልነበር መገንዘብ ይቻላል። የአፄው አገዛዝና የመንግስቱ መኪና እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ፣ በተጨማሪም የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው የገዢ መደብ በካፒታሊስት የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ የተካተተ ቢሆንም የራሱ የሆነ ነፃነት(Relative Autonomy) የነበረውና በዓለም አቀፍ ደረጃም ከሞላ ጎደል የሚከበር ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። እስከተወሰነ ድረስ ፊዩዳላዊ ሞራልም ስለነበር እንደወያኔውና እንደ አቢይ አሀመድ አገዛዝ አረመኔያዊ አልነበረም። በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ የነበሩት ወታደሮችና ፖሊሶች የራሳቸውን ገደብ የሚያውቁ ነበሩ። እንደዛሬው በአንድ ግለሰብ የማይጠመዝዙ በመሆናቸውና ጎሳዊ ስሜትም ስላልነበራቸው የአገራዊና ብሄራዊ ስሜት የነበራቸው ናቸው ማለት ይቻላል። እንደፈለገው አንድ ፖሊስ አንድን ግለሰብ ሆነ ወይም ብዙ ሰዎችን የሚያሰቃይበት ሁኔታ አልነበረም።
የደርግን አገዛዝ ልዩ የሚያደርገው በአብዮቱ ዘመን የተፈጠረው የተመሰቃቀለ ሁኔታና ከአገዛዙ ውጭ የነበረው በአብዛኛው መልኩ ኢ-ዲሞክራሲያዊና አገር አፍራሽ የሆነ ኃይልና ሁኔታዎችን ማንበብ ያልቻለው በግራና በነፃነት ስም የሚካሄደው እንቅስቃሴና ግፊት ጨቋኝ እንዲሆን እንደገፋፋው መገንዝብ ይችላል። እንደሚታወቀው ደርግ ስልጣንን ሲረከብ የመንግስቱን መኪና እንዳለ የተረከበ ወይም የነጠቀ በመሆኑና፣ ራሱም ደርግ የሚባለው ኃይል ሰፋ ባለ ጭንቅላትን በሚቀርጽና በሚያዳብር ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላለፈ በመሆኑ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ዘመናዊ ከሚባለው ጋር በሚጋጭበት ጊዜ በስድሳኛውና በሰባኛው ዓመተ-ምህረት በአብዛኛዎቹ የደቡብና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች የሚታየው የፈላጭ ቆራጭነት ወይንም የአምባገነን አገዛዝ ሁኔታ በአገራችንም ሊፈጠር ችሏል። በሌላ ወገን ግን በአብዛኛዎቹ የላቲን አሜሪካ አገሮች ብቅ ብቅ ያሉት የወታደር አገዛዞች ኩሙኒዝምን አጥብቀው የሚጠሉና ዲሞክራሲያዊ ኖርሞችን እንዲዋጉ ተብለው በአሜሪካ የሚሊታሪ ሳይንስ በሚሉትና በስለላ ድርጅቱ የሰለጠኑ በመሆናቸው፣ በመሰረቱ በጭቆና መንፈስ የተኮተኮቱ በመሆናቸው እንደዚያ ዐይነት ዕልቂት ለማድረስ በቅተዋል። ተግባራዊ ያደርጉ የነበረው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲም ከውስጥ ለተስተካከለ ዕድገት፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መዳበር የማያመች በመሆኑ የየመንግስታቱ መኪና የበለጠ ፋሺሽታዊ በመሆን ዲሞክራሲያዊ ኖርሞችን የሚያፍን ሆነ። እንደሚታወቀው ግሎባል ካፒታሊዝም ከሶስተኛው ዓለም ተብለው ከሚጠሩ አገሮች ሀብት ወደ ካፒታሊስት አገሮች ሊያስተላልፍ የሚችለው በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጨቋኝና ፋሺሽታዊ አገዛዞች ሲኖሩ ብቻ ነው። በዚህም አማካይነት የተወሰነው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት በዚህ ዐይነቱ የጭቆና ሎጂክ ውስጥ በመካተትና ራሱን ከአገሩና ከህዝቡ በመነጠል በቀላሉ በአሜሪካን ካፒታሊዝም በሚመራው ግሎባል ካፒታሊዝም የሚጠመዘዝ በመሆኑ የጭቆናውና የፀረ-ዕድገቱ አንድ አካል ነው። ስለሆነም ከራሱ ጥቅምና ኑሮ ባሻገር የማያይ በመሆኑ ህብረተስብአዊ ኃላፊነት የማይሰማው ሆነ። በዚህ መልክ በግሎባል ካፒታሊዝምና በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የአመጽ ሎጂክ ውስጥ የተኮተኮተውና የተካተተው የመንግስት መኪናና አገዛዙ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኤሊቱ ድህነትንና የስራ-አጥነትን የሚፈለፍል፣ በዕዳ አማካይነት ሀብት ከላቲን አሜሪካ አገሮች ወደ አሜሪካን ትላልቅ ባንኮች የሚያስተላልፍ በመሆን አገራዊና ብሄራዊ ባህርይ የሌለው ኤሊት ለመሆን በቃ።
ወደ ደርጉ አምባገነናዊ አገዛዝ ስንመጣ ከአብዮቱ ጋር መያያዙና፣ በተለይም ደግሞ እንደመሬት ለአራሹ የመሳሰሉት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተግባራዊ መሆናቸውና፣ በተጨማሪም ገበሬው የመሰባሰብ ወይም የመደራጀት መብት ማግኘቱ የደርግን አገዛዝ ለየት ያደርገዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በመንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉት ትላልቅ ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች አብዮታዊና ሶሻሊስታዊ የሚባሉትን መጠሪያዎች እንዲከናነብ ሊያደርጉት ችለዋል። ከዚህ ዐይነቱ በተግባር ከሚታይ ድርጊት ውጭ የደርግ አገዛዝ ከማርክሲስት ቲዎሪና ከሶሻሊስታዊ ርዕዮተ-ዓለም አንፃር ሲታይ አብዮታዊ ሊያሰኘው የሚያስችል አንዳችም ነገር አልነበረም። የማርክሲዝምን ወይም ሶሻሊስታዊ ቲዎሪን ለመረዳት ደግሞ የብዙ ዓመታት ጥናት የሚያስፈልግና ከሌሎችም ትችታዊ አስተሳሰብ ጋር መያያዝ ያለበት በመሆኑ አጠቃላይ በሆኑና በቀኖናዊ መልክ የቀረቡ ጽሁፎችን ብቻ በማንበብ መንፈስን ማነጽ አይቻልም። ስለዚህም ደርግ አምባገነናዊና አልፎ አልፎም አረመኔያዊ ዕርምጃዎችን መውሰዱ የሚያስደንቅ መስሎ ባይታይም፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት ራሱን ለመቆጣጠር አልቻለም። በዚህ ዐይነቱ አረመኒያዊ ተግባርስ አገርን ማዳን ይቻላል ወይ? ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ አልቻሉም። ይሁንና ሁኔታውን በጥብቅ ለተከታተለና እስከዛሬ ድረስ ዘልቆ የሚያነታርከንንና የሚያጫርሰንን ሁኔታ ቀረብ ብሎ ላጠና ሰው ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ፖለቲካዊ ድርጊቶች በጭንቅላታችን ውስጥ ሰርገው ለመግባት አለመቻላቸውን ነው የህብረተሰብአችን አወቃቀር የሚያረጋግጠው። በሌላ አነጋገር፣ አንድን አገርና ህዝብ በፈላጭ ቆራጭነት አስተሳሰብና አልበገርም በማለት መግዛት እንደማይቻል ነው። ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑና ጥበባዊ ባህርይም ያለው በመሆኑ አንድን ህብረተሰብ በጥበብ ብቻና ሁኔታዎችን በሚገባ በማጥናት ነው ማስተዳደር የሚቻለው። ከላይ እንዳልኩት በተፈጠረው ከአገዛዝ ውጭ በሆነ ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴና፣ ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ እንደ አሜሪካን በመሳሰሉት ማንኛውንም ዐይነት ለውጥ በሚጠሉት ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይሎች በመታገዙ ሳይወድ በግድ የደርግ አገዛዝ ጨቋኝና አምባገነን ወደመሆን ለማምራት ቻለ። ይሁንና ግን የደርግ አገዛዝ ከወያኔና ከዛሬው በአቢይ አህመድ ከሚዘወረው የብልጽግና አገዛዝና የመንግስቱ መኪና ጋር ሲወዳደር የራሱ የሆነ ነፃነት ነበረው። በአብዮታዊ እርምጃዎች የተነሳ አነሰም በዛም ከግሎባል ካፒታሊዝም ቁጥጥር ውጭ የሚንሳቀስና በብድር ያልተበተበ፣ በነበረውም ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ከሚባሉት፣ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ከመሳሰሉት ብድር የማግኘት ዕድል አልነበረውም። ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ስንነሳ የራሱ የሆነ ነፃነት የነበረውና ብሄራዊ ነፃነትን የማያስደፍር ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።
ወደ ወያኔ አገዛዝ ስንመጣ በመሰረቱ ስልጣን ላይ የተቀመጠው የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስቶችን አገርን የማዳከምና የመበታተን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ ነው። ስለሆነም በአፄ ኃይለስላሴና በደርግ ዘመን የተዋቀረውን የመንግስት መኪና ለራሱ በሚስማማ መንገድ በማዋቀርና በራሱ ካድሬዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ በማድረግ ወደ ዘራፊነት የተሸጋገረ አገዛዝ ነው። ዘራፊነቱንም ሊያጧጥፈው የቻለው በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው በሚጠሩት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ሲሆን፣ ይህ ፖሊሲ በአንድ በኩል የወያኔ ካድሬዎችን ሲያደልብ፣ በሌላ ወገን ባልተስተካከለ ንግድና ዕዳ አማካይነት ሀብት ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ካፒታሊስት አገሮች ሊሸሽ የቻለበትን ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረጉ ነው። በተለይም ወያኔን አጥብቀው የሚጠሉትና የጎሳ ፌዴራልዝም ተግባራዊ በማድረጉ የሚከሱት ታጋዮችና ፖለቲከኛ ነን ባዮች ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ሊረዱና ሊገባቸው የማይፈልጉት ወያኔ የአሜሪካኖችና የእንግሊዝ ኦሊጋርኪ መደብ ቅምጥ መንግስት የሆነና ከዋሽንግተን ረቆ በመጣው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የዘራፊትንና የአዘራፊነትን ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው። በሌላ አነጋር፣ ወያኔ በአገራችን ምድር ተግባራዊ ያደረጋቸው አገርን የሚያፈራርስና ድህነትን የሚያስፋፋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍልን በማደለብና ብልግናን የሚያስፋፋ ፖሊሲ ከአሜሪካና ከተቀረው የውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ነው በአብዛኛዎቹ ታጋይ ነን ባዮች የሚታመነው። ይህም ማለት ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ረግጦ ሲገዛ፣ ህዝባችንን ሲገድል፣ በጎሳና በቋንቋ ከልሎ በህዝብ ዘንድ አለመተማመን ሲፈጠር ይህ ሁሉ የተጠነሰሰውና ተግባራዊ ለመሆን የበቃው በራሱ በወያኔ ብቻ ነው፤ ስለሆነም አሜሪካንና የተቀሩትን የካፒታሊስት አገሮች መወንጀሉ ትክክል አይደለም እያሉን የሚታዩ ነገሮችንና በሳይንስ ሊረጋገጡ የሚችሉ ነገሮችን አምነን እንዳንቀበል ያላደረጉት ጥረት የለም። የግሪክ ፈላስፎች እንደሚሉት አዕምሮ ማየት ካልቻለ ዐይንም ማየት አይችልም ብለው እንደሚያስተምሩን ለአብዛኛዎቻችን በግልጽ የሚታዩ ነገሮች እንዳይታዩንና ጥያቄም እንዳናቀርብ ለመገደድ ችለናል። ሰለሆነም በህዝባችን ላይ የደረሱት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮሎጂያዊ ቀውሶች በሙሉ ሊታዩን በፍጹም አልቻሉም ። ይህም የሚያረጋግጠው ከዕውነተኛ የነፃነት ትግል አንፃር የእነዚህ ታጋዮች ትግል ያልተሟላ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።
ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የወያኔን አገዛዝ እንቃወማለን፣ እንታገላለንም የሚሉት በሙሉ ፖለቲካቸውን ለመረዳትና መንፈሳቸው በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መታነጹን ለማወቅ እንቸገራለን። ከዚህም በሻገር ትግላቸው ብሄራዊ የሆነና የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ህዝባችንንም ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል ሁለ-ገብ ፖሊሲ ያላቸው ለመሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ ነው። ስለሆነም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሎጂክ ውጭ ለአገራችን የተሟላ ዕድገት፣ ለብሄራዊ ነፃነትና ለዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መታገላቸውን እንድንጠራጠር አድርጎኛል። ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ህዝባችንና አገራችንን ረግጦ ሲገዛ ግልጽና ሰፊው ህዝብ እንዲረዳው የሚያደርግ ደረጃ በደረጃ፣ ከመንግስት መኪና አወቃቀር አንስቶ እስከ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ድረስ ትንተና መስጠት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ትግሉ የተሟላና በቲዎሪና በሳይንስ ያልተደገፈ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል። ወያኔ ከስልጣን ላይ ከተነሳ በኋላ እሱን የሚተካው አገዛዝ ደግሞ ምን ምን ነገሮችን በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የነደፈው አስተሳሰብና በጽሁፍ ያስቀመጠው አንዳችም ነገር አልነበረም። ይጠብቅ የነበረው አዲሱ አገዛዝ ምን ያደርግ እንደነበር ነው። ተስፋ የሚጣልበትና ሊበራል የሆነ አገዛዝ ስልጣንን የተረከበ እንደሆነ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ለመታመን በቅቷል።
ወደ አቢይ የብልጽግናው አገዛዝ ስንመጣ ወደ ውጭ ሊበራል መስሎ ስልጣንን ሊጨብጥ የቻለ ኃይል ሲሆን፣ እዚያው በዚያው ግን እያሳሳቀና እያታለለ ወደ ገዳይነት፣ ወደ ማፈናቅል፣ ማንነትን ተኮር ወዳደረገ ጭፍጨፋና በቀጥታና በግልጽ ወደ ዝርፊያ የተዘዋወረ አገዛዝ ነው ማለት ይቻላል። የአቢይን አገዛዝ ከወያኔው የሚለየው በግልጽ ሁለንታዊ የሆነ የባህል ጦርነት መክፈቱና፣ በተለይም በጴንጤ ቆንጠ ሃይማኖት ተከታዮች በመታቀፍ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ግልጽ የሆነ ጦርነት ማወጁ ነው። ሌላው በመሀከላቸው ያለው ልዩነት ወያኔ ከ17 ዓመታት የበረሃ የጦር ትግል በኋላ በአሜሪካን የስለላ ድርጀት አማካይነት የኢትዮጵያን የፀጥታ ኃይል በማንኮታኮትና በወታደሩ ውስጥ ያለውን ግኑኝነት በመበጣጠስ ስልጣን ላይ እንዲወጣ አመቺ ሁኔታ ማግኘቱ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ግን አቢይና አጋሮቹ የወያኔን ጡት እየጠቡ ያደጉና በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላታቸው የተኮተኮተ ስለሆነ ስልጣንን ሲጨብጡ የተሳሳተ ትረካቸውን መሰረት በማድረግ ነው ለእነሱ በሚስማማ መንገድ አገራችንን መበወዝ የጀመሩት። ይህም ማለት፣ እነአቢይና አሁን በአጠቃላይ ሲታይ የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች በጭንቅላታቸው ውስጥ ሲያብሰለስሉ የነበሩት ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ከአማራው ብሄረሰብ በተውጣጣ የገዢ መደብ ስትገዛ የነበረችና፣ ይህም መደብ የአማራውን ብሄረሰብ ጥቅም ብቻ በማስጠበቅ ሌሎችን ይጨቁን የነበረ ነው የሚል ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጣው የገዢ መደብ ሌሎችን አካባቢዎች የቅኝ ግዛት በማድረግና በመበዝበዝ ዕድገታቸውን እንዳሰናከለባቸው ነው። ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ትረካ ደግሞ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ አወቃቀር ጋር የማይጣጣም ብቻ ሳይሆን ኢ-ሳይንሳዊም ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የገዢ መደቡን ስብጥር ስንመለከት ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጣ ብቻ አልነበረም። በጊዜው በነበሩት አገዛዞች፣ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ድረስ ያሉትን አገዛዞች ስንመለከት አማራውን ብቻ እንጠቅማለን፤ በኢኮኖሚና በባህልም እንዲያድግ እናደርገዋለን፤ በአንፃሩ ደግሞ ሌላውን አቀጭጨን እናስቀረዋለን በማለት የተነሱ አልነበሩም። የሁለቱም አገዛዞች አካሄድ አንድን አገርና ህብረተሰብ ለመመስረትና በአንድ ባንዲራ ስር በማምጣት ቀስ በቀስ ዕድገትን ለማምጣት የተወሰደ እርምጃ ነበር። በተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል እጦትና በነበራቸው በጣም ደካማ የሆነ የምሁራዊ መሰረት ከታች ወደ ላይ መደረግ የነበረባቸውን የህብረተሰብ ግንባታ በቅደም ተከተል ማካሄድ አልቻሉም። በዘመናዊነት ስም የገቡት የጥገና ለውጦች በህዝቡ ዘንድ መቀራረብንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ አንዳንድ ለአገር ወዳድነትና ለብሄራዊ አንድነት የሚሆኑ ነገሮች ተግባራዊ ቢሆኑም ጠንካራና አገር አቀፍ፣ እንዲሁም ፈጣሪ የሆነ የህብረተስብ ክፍል ሊፈልቅ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአፄ ምኒልክና የአፄ ኃይለስላሴ የጥገና ለውጦች ለስር ነቀል ለወጥ ወይም ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለሚደገፍ የካፒታሊስት ስልተ-ምርት የሚያመች አልነበረም። ሰፋ ያለና አገር አቀፍ የሆነ የኢኮኖሚ ግንባታ በሌለብት፣ ከተማዎችና መንደሮች በተስተካከለ መልክ ባልተገነቡበት አገርና፣ እነዚህም በተለያዩ የመመላለሻና የመገናኛ ዘዴዎች ባልተያያዙበት አገር ስለኔሽን ቢልዲንግ(Nation Building) ማውራት በፍጹም አይቻልም።
ያም ተባለ ይህ የኔሽን ቢልዲንግ አለመጠነቃቅ ወይም ወደዚያ የሚያመራ ሁኔታ አለመፈጠር በሁለቱ አገዛዞች የሚሳበብ አይደለም። ችግሩ ራሱ የመነጨው አስቸጋሪ የሆነው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ሂደትና ይህንን በሰፊው ሊያጠና የሚችል ምሁራዊ ኃይል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብቅ ለማለት ባለመቻሉ ነው። የተገለጸለትና በሁሉም አቅጣጫ የታጠቀ ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ ደግሞ አንድን አገርና ህዝብ መስመር ማስያዝ አይቻልም፤ በአገዛዙም ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ጥገናዊ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ በፍጹም አይቻልም። ከዚህ ሳይንሳዊ ሀቅ ስንነሳ የወያኔዎችና የእነ አቢይ ውንጀላ መሰረተቢስ ነው። በማንኛውም የዕውቀት መለኪያ ሊደገፍ የሚችል አይደለም። ከተሳሳተ ትረካ በመነሳት ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚል ደግሞ ንጹህ በንጹህ የቂም-በቀል ፖለቲካ በማካሄድ የታሪክን ሂደት ያጣምማል። በኢምፔሪያሊስቶች ጉያ ስር በመሸሸግና የእነሱ ታዛዥ በመሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተሟላ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን ያግዳል። በዚያው መጠንም በጉልበትና በማንአለኝበት መንፈስ በመወጠር ህዝቡ ግራ ተጋብቶ እንዲኖር ብቻ ማድረጉ ሳይሆን በጎሪጥ እንዲተያይ ያደርገዋል። በጋራ ተነሳስቶ አገሩን ለመገንባት እንዳይችል እንቅፋት ይሆንበታል።
ባጭሩ በዚህ መልክ የሚካሄድ የተሳሳተ ትረካና ይህን መሰረት በማድረግ ስልጣን ላይ መውጣት ይኸው እንደምናየው ከአራት ዓመት በላይ የፈጀ መፈናቀል፣ ማንነትን ያተኮረ ጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄድና በዚህም አማካይነት የምዝበራ ተግባር መፈጸም ነው። በዚህ ዐይነቱ አረመኒያዊ ተግባሩ ለመግፋት ደግሞ ከሚሊታሪው አንስቶ እስከፖሊሱና እስከጸጥታው ድረስ ያሉትን የጭቆና ተቋማት በቂ ዕውቀትና የህብረተሰብ ታሪክ ግንዛቤ በሌላቸው የኦሮሞ ብሄረሰቦች ሰግስጓል። ይህንን ተገን በማድረግም የዘረፋ መረብ በመዘርጋት በተለይም በአዲስ አበባና በአካባቢው ባሉት ትናንሽ ከተሞች ውስጥ የኦሮሞ ኤሊት መሬትን እንዲቆጣጠር በማድረግና የደሃውን ቤት በማፈራረስ ሀብትን ወደ መቆጣጠር እያመራ ነው። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሆነችው አዳነች አበቤ ይህን ዐይነቱን የንጥቂያ ተግባር የምታስፈጽም ነች። እየመረጠች የአማራዎችንና የጉራጌዎችን ቤቶች እንዲፈርሱ ለካድሬዎቿ ትዕዛዝ ሰጥታለች፤ በተግባርም እያስፈጸመች ነው። ከዚህም አልፋ በመሄድ በየትምህርትቤቱ ውስጥ የኦሮሞ ባንዲራ መሰቀል አለበት፣ በኦሮምኛም መዝሙር መዘመር አለብት ብላ ተማሪዎችን ማስጨነቅ ኢትዮጵያን የሚቆጣጠረው አዲሱ የኦሮሞ ኤሊት ኢትዮጵያ የምታበለው አገርና፣ በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ እንዴት እንደተመሰረቱና እንደተረቆሩ አለማወቃቸውን ነው የሚያረጋግጠው። እንደሚታወቀው አንድ አገርና ህብረተሰብ የውጣ ውረድ ትግል፣ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ የማሰብ ኃይል ውጤቶች በመሆናቸው ከተለያዩ አካባቢ በመጡ ሰዎች ወይም ህዝብ የሚመሰረቱ ናቸው። ከዚህ ውስጥ ነገስታትና በገዢው መድብ ውስጥ የሚካተቱትና እንደሃይማኖት የመሳሰሉት ነገሮች ለህብረተሰብና ለአገር ምስረታ የየራሳቸውን አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ገበሬውና አንጥረኛውም የየበኩላቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል። በተለይም እንደምግብ የመሳሳሉ ባህላዊ ነገሮች ሊሰሩ የ´ሚችሉት ገበሬው እያመረተ በሚያቀርበው የተለያዩ የሰብል ዐይነቶች ነው። በተለያየ የታሪክ ወቅት የኖሩ እናቶቻችንም የምግብና እንደጠላ፣ ጠጅና ካቲካላ የመሳሰሉትን ባህላዊ ነገሮች በመፍጠርና በማዳበደር ለአገርና ለህብረተሰብ ምስረታ የበኩላቸውን አበርክተዋል። ስለሆነም ስለአገርና ህብረተሰብ ምስረታ በምናወራበት ጊዜ ማታ ተቦክቶ በተነጋታው እንደሚጋገር እንጀራ ወይም ዳቦ ሳይሆን ማየት ያለብን የውጣ ውረድና የአስጨናቂ ትግል ውጤቶች መሆናቸውን ነው። ወደ ከተማዎች ምስረታም ስንመጣ ከአንድ ጎሳ ብቻ በተውጣጡ ሰዎች የተዋቀሩበት ጊዜ የለም፤ በታሪክም ውስጥ አልታየም። ከተማን ከተማ የሚያሰኘው ልዩ ልዩ ዕውቀቶች፣ እንደ ዕደጥበብ፣ ሙዚቃና አርት፣ አርኪቴክቸርና ልዩ ልዩ የፈጠራ ስራዎች፣ አልፎም ቡና ቤቶች፣ መዝናኛዎችና ሌሎችም ነገሮች ሲስፋፉና ለሰፊው ህዝብ ግልጋሎት ሲሰጡ አንድን ከተማ በዕርግጥም ከተማ ያሰኛታል። ይህ ዐይነቱ ዕድገት ደግሞ የብዙ ዓመታት ውጤትና፣ ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ሰዎች አስተዋፅዖ ነው። ሰለሆነም ፍንፍኔ የምትባለውን ከተማ ኦሮሞዎች ናቸው የቆረቆሩት፣ ስለሆነም ሌላውን ጎሳ በሙሉ በማባረር የኦሮሞዎች ከተማ ብቻ እናደርጋታለን ማለት ያላዋቂነትና የኋላ-ቀርነት ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ ከወራሪነትም ባህርይ አለመላቀቅ ነው።
ለማንኛውም ከጭቆና መኪናው ባሻገር ያለውን የአቢይን አገዛዝ ውስጣዊ መዋቅር በምንመረምርበት ጊዜ አንዳንዶቹ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ስልጣን የጨበጡና በዘረፋ ተግባር ራሳቸውን ያበለጸጉ ናቸው። ከዚህ ውስጥ የድሮው ኢንዱስትሪ ምኒስተር ግርማ ብሩና አባዱላ ገመዳ ይገኙባቸዋል። ከዚህ ውጭ የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት ይጋልብባቸው የነበሩት እንደ ሌንጮ ባቲና ሌሎችም የአገዛዙ አካልና አማካሪ በመሆን ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ለሚካሄድው የጭፍጨፋ፣ የማውደም፣ የዝርፊያና አገርን እንዳለ የመበወዝ ተግባር ውስጥ ተካፋይና በግንባር-ቀድምትነት የተሰለፉ ናቸው። ኢትዮጵያን እንዳለች ወደ ኦሮሚያ እንለውጣለን ብለው የተነሱ ፋሺሽታዊ ኃይሎች ናቸው። የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ወያኔ ተግባራዊ ያደርግ የነበረውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስመልክቼ “የነፃ ገበያ ወይም ካፒታሊዝም” በሚል አርዕስት ስር ከ20 ገጽ በላይ የሆነ ሰፊ ሀታት ጽፌ ነበር። በጊዜው ሌንጮ ባቲ ጽህፌን ካነበበ በኋላ እስካሁን ድረስ በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ሳይገባን ነበር የተደረጉት፣ አንተ ብዙ ነገሮችን ግልጽ አድርገህ በሶስት ቅፅ የተጻፈውን የማርክስን ዳስ ካፒታል ስራ አቀረብክልን በሚል የሙገሳ ጽሁፍ በኢሜይል እንደላከልኝ ትዝ ይለኛል። ይህ ሰው ተቀልብሶ አቢይ ስልጣን ከያዘ በኋላ “ለሶስት ሺህ ዓመት ያህል ያጣነውን ዕድል ዛሬ አግኝተናል፤ ከእጃችን እንዳይወጣ አጥብቀን መስራት አለብን” በማለት ለኦሮሞ ኤሊቶች ሲናገር ሰምቼዋለሁ።
ለማንኛውም ከአቢይ ጀምሮ እነዚህንና እስከ ኦሮሚያ ክልል ድረስ ያለውን የአገዛዝ ሂራርኪ ስንመለከት እነዚህ ኃይሎች በሙሉ ምንም ዐይነት ምሁራዊ መሰረት የሌላቸውና የሚያደርጉትንም የሚያውቁ አይደሉም። ተጨቁነን ነበርን ከማለት በስተቀር በራሳቸው ጥረት ያዳበሩት ሳይንሳዊ ቲዎሪና የፍልስፍና መሰረት የላቸውም። እስከዛሬም ድረስ አንዳችም ሳይንሳዊ ጽሁፍ ያላበረከቱ ናቸው። ምን ዐይነት የኢኮኖሚም ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም የሚያውቁት ነገር የለም። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በእነ ዓለም ባንክ የተነደፈውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አሁንም ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸውን የሚያደልቡና የአገራችንን ሀብት በውጭ ዘራፊዎች እንዲዘረፍ የሚያደርጉ ናቸው ማለት ይቻላል። አማካሪዎቻቸውም እንደ ዘመዴነህ ንጋቱ የመሳሰሉት የተትረፈረፈ የጥሬ ሀብት ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ካፒታል፣ በተለይም በአሜሪካኖች የኢንቬስትሜንት ባንኮች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁና እንዲዘረፉ የሚያደርገው፣ የወያኔን አገዛዝ ሲያማክር በነበረውና ጭንቅላቱ በጨው በታጠበ አደገኛ ሰው ነው። አቢይ አህመድ ልክ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ፕሬዚደንት ባይደን ባዘጋጁት ሰሚናር ላይ ተገኝቶ ከተመለሰ በኋላ ብዙ ለውጥ እንዳመጣ ይኸው ዘመዴነህ ንጋቱ ከሀቁ የራቀ ሀተታ በመስጠት ብዙ የዋህ ወጣት ኢትጵያውያንን ሲያሳስት ሰምቼዋለህ። አቢይ ከአሜሪካን ጉዞው ከተመለሰ በኋላ ምን ዐይነት ለውጥ ተግባራዊ እንዳደረገ ግን በግልጽ አልነገረንም። በየቀኑ ከአገር ቤት የሚደርሱን ዜናዎች የሚያረጋግጡልን ለውጥን ሳይሆን በጅምላ መገደልንና መፈናቀልን እንደሆነ ዘመዴነህ ንጋቱ የተረዳው አይመስልም። ሰውየውም ስለሰው ህይወት ሳይሆን ስለገንዘብ ብቻ የሚያስበ ስለሆነ፣ ለአቢይ የተገባለትን የገንዝብ ዕርዳታ እንደለውጥ አይቶት ከሆነ በጣም ተሳስቷል። ይህ ሰው ሳይንሳዊውን የመዋዕለ-ነዋይ ህግ በመጣስ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት አገሮች የጥሬ-ሀብት አምራች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ ሌት ተቀን የሚሰራ ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገትና የአገር ውስጥ ገበያን መዳበር የሚቀናቀንና፣ በተለያዩ ሰንሰለቶችም እንዳይተሳሰሩ የሚታገል ነው። ህዝባችን ደሃና አቅመ-ቢስ ሆኖ እንዲቀር ነው አስተሳሰቡ።
በአጭሩ እነዚህ ሁሉ ኃይሎች በአንድ በኩል ከውጭ በዕዳ መልክ የሚፈሰውን ገንዘብ የተወሰነውን በመዝረፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከውስጥ በቀረጥ አማካይነት የሚሰበሰበውን ገንዘብ በተሳሳተ የበጀት አመዳደብ ወደ ዝርፊያ የገቡ ናቸው። ከዚህም በላይ ተራው ገበሬ እያመረተ የሚያቀርበውን ምርትና እያደለበ የሚሸጠውን በሬና በግ በመመገብ ወደ ተራ ውንብድናና አገር አውዳሚነት የተሸጋገሩ ናቸው። በአጭሩ ማለት የሚቻለው የአቢይ አህመድ አገዛዝና የተቀሩት የኦሮሞ ኤሊቶች በአጠቃላይ ሲታይ በህዝብ ሀብት እየተመገቡና እየደለቡ በዚያው መጠንም በከፍተኛ ደረጃና ፍጥነት አገራችንን እያውደሙ የሚገኙ ናቸው። በዚህ ድርጊታቸው ደግሞ ዓለምን የሚያከረባብተውና ጦርነትን ዓለምአቀፋዊ ያደረገው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና አጋሮቹ ያግዟቸዋል ማለት ይቻላል።
ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ወጥተን የእሮምያ ክልል የሚባለውንና አስተዳደሩን ስንመለከት በከፍተኛ ጭፍጨፋ ውስጥ የሚሳተፍ ፋሺሽታዊ አገዛዝ እንደሰፈነ እንመለከታለን። የአርቲፊሻል ስም በተሰጠው የኦሮምያ ክልል በሚባለው ውስጥ ኦሮሞዎች በዚያ አካባቢ ከመስፋፋታቸው በፊት የሌሎች ብሄረሰቦች ግዛት የሆነና፣ በአንዳንድ አካባቢም ከአስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ከአማራው ክፍል ወደዚያ በመላክ የሃማኖት ትምህርት ሲያስተምሩ እንደነበር ይታወቃል። አብዛኛዎቹ በመጋባትና በመዋለድ በብዙ መቶ ዓመታት ያስቆጠረ ትውልድ በተከታታይነት ሊፈጠር ችሏል። ይህንን ትተን በአሁኑ ወቅት ክሌሎች ብሄረሰቦች ባሻገር ወደ አስር ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር አማራ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ይኖራል። አብዛኛዎች በንግድ ስራ፣ በእርሻና በሌሎችም ሙያዎች በመሰማራት ቀረጥ የሚከፍሉና ሀብትን ለተቀረው ለኗሪው ህዝብ የሚፈጥሩ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ኃይሎች ቀረጥ እየከፈሉና ሀብትን እየፈጠሩ በኦሮሞ የአስተዳደርና በፓርሊያሜንቱ ውስጥ ተወካይነትና ተጠሪነት የላቸ´ውም። በፖሊሲና በልዩ ኃይልም ውስጥም የመቀጠር መብት የላቸውም። ይህም የሚያሳየው የሚወክላቸው ሳይኖር ቀረጥ(Taxation without Representation) ዝም ብለው የሚከፍሉ ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ እነሺመልስ አብዲሳ የአፓርታይድ ስርዓት መስርተዋል። ይገርማል ጥቁር ሰው በወገኑ በጥቁሩ ህዝብ ላይ እንደዚህ ዐይነት አሳፋሪ ስርዓት ሲመሰርትና በደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ስርዓት ዘመን እንኳን ያልታየ ጭፍጨፋ ሲያካሄድ። ክልል ብለው የሚጠሩት በጉልበት የተያዘና ህጋዊ የተደረገ በመሆኑ ይህንን ዐይነቱን ኢ-ሰብአዊና ታሪክን ያጣመመ ሁኔታ በአንዳች መንገድ የግዴታ መቀልበስና ጠቅላላውን ህዝብ የሚወክል ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መገንባት የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው እላለሁ። ከዚህም በላይ የኦሮምያ ልዩ ኃይል የሚባለው በሺመልስ አብዲሳ ቁጥጠ ስር ያለው ሰራዊት እንዳለ መበተን አለበት። ሺመልስ አብዲሳ በመንግስት ላይ ሌላ መንግስት በመመስረትና በሌሎች ክልሎችም ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሚፈተፍት ነው። ለማንኛውም ኦሮሞዎች መሬቱን፣ ወንዞችን፣ ዛፎችንና ሁሉን የተፈጥሮ ነገሮች በሙሉ የፈጠሯቸው ይመስል የሰውን መሬት ከወረሩ በኋላ የእኛ ነው በማለት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ፍዳቸውን እያሳዩ ነው። ይህንን ዐይነቱን የአንድን አገር ታሪክ የናደና ህብረተሰቡ በስምምነት እንዳይኖር የሚያደርግ አስተዳደርን ዝም ብሎ መመልከት የወንጀሉ ተባባሪ እንደመሆን ያስቆጥራል። በአጠቃላይ ሲታይ በፌዴራል ደረጃና በየክልሎቹ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት አገራችንና ህዝባችን በሰለጠኑ ሰዎች እንደማይተዳደሩ ነው። በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት ችግር አለ። ሎጂካዊ በሆነ መልክ የማሰብ ችግር አለባቸው። አብዛኛዎቹ የአገራችን መሪዎች ሰዎች መሆናቸውንም የተረዱ አይመስለኝም። አንዳንዶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አጠናቀናል፣ የዶክትሬት ዲግሪም አለን ቢሉ ሁሉም ያልተገለጸላቸውና ኋላ-ቀር የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው በመሆናቸው አገራችንና ህዝባችንን ወዴት እንደሚወስዱዋቸው የሚያውቁት ነገር የለም። አብዛኛዎቹም ከልዩ ልዩ ጭንቅላትን ከሚገነቡ የስነ-ጽሁፍ፣ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መጽሀፎች የራቁ ስለሆነና ስለማያነቡም መንፈሳቸውን ለማደስና ጥያቄም ለመጠየቅ የሚችሉ አይደሉም። ደስታ የሚሰጣቸው ስልጣን ላይ መቆየትና ህዝብን ማሰቃየት ብቻ ነው። ስለሆነም በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የሰፈነው አገዛዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት አገዛዞች ጋር ሲወዳደር በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝና ራሱን የሸጠ አገዛዝ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። በማንኛውም የአፍሪካ አገርም እንደዚህ ዐይነት አረመኔያዊ አገዛዝ በፍጹም አይታይም። ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ የሚያስቆጥር ታሪክ ባለው አገር ውስጥ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን እንደዚህ ዐይነት ፈሺሽታዊና አረመኔያዊ አገዛዝ ሲሰፍን ሁላችንም ማፈር አለብን። እንዴት እንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ከአንዴም ሁለቴም ጭምር ሊፈጠር ቻለ? ብለን ለመጠየቅ በፍጹም አልቻልንም።
ነገሩን ለመዝጋት ያህል የኢትዮጵያን የመንግስት አወቃቀር፣ በተለይም ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ እስከ አቢይ አገዛዝ ድረስ ያለውን የዛሬውን ሁኔታ ስንመለከት የህብረተሰባችን ዋናው የኢኮኖሚ መሰረት እርሻና የአገልግሎት መስኩ ናቸው። በተለይም ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት ይበልጥ የአገልግሎቱ መስክ ነው እያደገና እየተስፋፋ ለመምጣት የቻለው። የአገልግሎት መስኩ በተንዛዛበት አገርና ብዙም ውጣ ውረድ ሳይኖር በቀላሉ ሀብት በሚፈራበት አገር ውስጥ ደግሞ ፈጣሪ የሆነና በቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ የሚሰማራ የከበርቴ መደብና የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል መፍጠር አይቻልም። ስለሆነም አንድ አገዛዝና ህዝብ ዋናው የኢኮኖሚ መሰረቱ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ዕድገትና መስፋፋት ሳይሆን የአገልግሎት መስኩ ዋናው የገቢ ምንጭ በሚሆንበት አገር ውስጥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለማድረግ የሚችል የህብረተሰብ ክፍል መፍጠር አይቻልም። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ደግሞ አገዛዙና የመንግስቱን መኪና የበለጠ ፋሺሽታዊ ያደርጋቸዋል ማለት ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ትግል በሚካሄድበት ጊዜ በነገሮች መሀከል ያለውን ትስስር መረዳትና፣ ካለ መሰረታዊ ለውጥ የተረጋጋ አገር መገንባት እንደማይቻል ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
የመንግስትን ሚናና ኃላፊነት የመረዳት ችግር !
ቀደም ብዬ አጠር መጠን ባለ መልክ ሰለካፒታሊስት የመንግስት አወቃቀርና ሚና አንዳንድ ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ይህንን ዐይነቱን ትንተና በተለያየ ጊዜያት ለማስረዳት ብሞክርም በአብዛኛዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ የተቀረጸ ነገር ስላለ የካፒታሊዝምን መንግስት ሚና ለመረዳት ከፍተኛ ችግር አለ። በሌላ አነጋገር፣ መንግስት እንዳለ ሆኖ´ ዋናው ነገር ግን የሚካሄደው በነፃ ገበያ አማካይነት ነው የሚል አስተሳሰብ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ አስተሳሰብ ሆኗል።
ለማንኛውም ካፒታሊዝም ዛሬ እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው በተለይም ክ1648 ዓ.ም ጀምሮ የህብረ-ብሄር ምስረታ አስፈላጊነት ግንዛቤ ውስጥ ከገባ ጀምሮ ነው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የህብረ-ብሄር አስተሳሰብ ስላለነበር በአውሮፓ አገሮች መሀከል የጦርነት መንፈስ ያየለበትና ጠንካራ ነኝ የሚለው ሌላውን የሚወርበት ዘመን ነበር። ከዌስት ፋሊያ ስምምነት ከ1648 ዓ.ም በኋላ በተደረሰው ስምምነት መሰረት የፍጹም ሞናርኪ አገዛዞችና ምሁራን ለአንድ አገር ጥንካሬ መኖር በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባት ነው በሚል በዚህ ላይ ርብርቦሽ ያደርጋሉ። የኢኮኖሚውም ፖሊሲ መርከንታሊዝም(Mercantilism) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን((Infant Industries) በተለያዩ የታሪፍና ታሪፍ-ነክ ባልሆኑ ነገሮች በመከላከል እንዲያድጉና እንዲስፋፉ ማገዝ፤ ከዚህም በላይ ኢንደስትሪየስ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ እንዲል አመቺ የሆነ ሁኔታን መፍጠር። በዚህ መልክ በፍጹም የሞናርኪዎች የአገዛዝ ዘመን የተነጠፈው የኢኮኖሚ አወቃቀር እነ አዳም ስሚዝ የነፃ ገበያ ብለው ለሚጠሩት መሰረት ጣለ። ይሁንና የካፒታሊዝምን ዕድገትና መስፋፋት ስንመለከት በተለያዩ ጊዜያት የመንግስታት ጣልቃ-ገብነት እንደየሁኔታው ከፍና ዝቅ ብልም እንዳለ የተዳከመ አልነበረም። በተለይም ከፍተኛ ቀውስ በሚታይበት ጊዜ ጣልቃ በመግባት ኢኮኖሚው እንዲያንስረራ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጎማ ያደርጋሉ። ከዚህ ውጭ ማንኛውም ህዝባዊ ባህርይ ያላቸው፤ እንደመንገድና መመላለሻ የመሳሰሉት፣ ትምህርትቤቶችና ክሊኒኮች፣ እንዲሁም የባህል ነከ ነገሮች በሙሉ በመንግስት ድጎማና ጣልቃ-ገብነት የሚደገፉና በየጊዜው የሚጠገኑ ናቸው። ይህም ማለት የካፒታሊስት መንግስታት መደባዊ ባህርይ ቢኖራቸውም ህብረተሰቡ ፈሩን እንዳይለቅና ህብረተሰብአዊ ግጭት እንዳይኖር ለህዝቡ የሚጠቅሙ ብዙ ነገሮችን ይሰራሉ ማለት ነው። አንዳችም ቦታ ላይ ህዝብን የሚከፋፍልና አገርን የሚያዳክም ስራ ሲሰሩ አይታይም። ከኢትዮጵያ ውጭ አብዛኛውን ዕድሜዬን እዚህ ምዕራብ ጀርመን ያሳለፍኩና የምኖር ስለሆነ ክማየውና፣ በልምድም ካካበትኩትና በቲዎሪም ደረጃ ባጠናሁት የማረጋግጠው ይህንን ሀቅ ነው። በማንኛውም ጊዜ ብቃትነት የሌለው አሰራርና ህዝብን የሚጎዳ ስራ ሲሰራ አላየሁም። ውስጣዊ ኃይል ያለውም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚካሄደው የኢኮኖሚ ዕድገትና ዓለም አቀፍ ተዋንያን የሆኑት ትላልቅ ኩባንያዎችም አይፈቅዱም። በተለይም በአሁኑ ወቅት በሰለጠነ የሰራተኛ እጦት የተነሳ ከውጭ አገሮች ወጣትና በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ሰዎች እንዲመጡ የሚጎተጉቱ የማዕከለኛ ኢንዱስትሪና የትላልቅ ኩባንያዎች ባለቤቶች ናቸው።
ነገሩን ግልጽ ለማድረግ በቴዎሪም ሆነ በተግባር እንደሚታየው መንግስት የሚባለውና የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው የገዢ መደብ የሚባለው ግልጽ ተግባሮችና ግዴታዎች አሉት ማለት ነው። 1ኛ) የአገሩን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት። ለዚህ ደግሞ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆኑ ማድረግ። ከዚህ የሚቀድመው ግን ድህነትንና ረሃብን ማስወገድ ነው። በተለይም በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተነሳ ከተማዎቻቸውና ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጭያዎችና ቤቶቻቸው የፈራረሱባቸው እንደጀርመን የመሳሰሉት አገሮች ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት ፖሊሲ ሁለ-ገብና፣ በተለይም ለህዝቡ መጠለያና በጣም አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት ነው።2ኛ) ከዚህ በመነሳት የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) እንዲዳብር ማድረግ ነው። 3ኛ) የሰው ኃይልና ዕውቀት እንዲሁም ካፒታል ከአንድ ቦታ ወደሌላው አካባቢ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር። 4ኛ) በሁሉም ክፍለ-ሀገር የከተማዎችን ዕድገት በተስተካከለ መንገድ መገንባት። የሰው ኃይል ፍሰት ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዳያመራ በተወሰኑ አካባቢዎች ወይም ከተማዎች ላይ ብቻ አለማትኮር። 4ኛ) የዕደ-ጥበብ ሙያ እንዲስፋፋ አመቺ ሁኔታን መፍጠር። ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በፈጠራ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ። 5ኛ) ማዕከለኛና ትናንሽ ኢንዱስትሪዎች በየቦታው እንዲቋቋሙ ማድረግ። ለዚህ የሚስማማ ደግሞ የብድር አሰጣጥ ዘዴ ማመቻቸት። በባንኮችና በአምራች ኢንዶትሪዎች መሀከል የበለጠ ግኑኘነት እንዲፈጠር ማድረግ። 6ኛ) ይህ ዐይነቱ ግኑኝነት የገንዘብን መሽክረከር ስለሚያፋጥነው(Velocity of Money) ገንዘቡም ውስጣዊ ጥንካሬ ስለሚያገኝ የመግዛት ኃይሉም ከፍ ይላል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከሰራተኛው የገቢ ዕድገት ጋር የሚያያዝ መሆን አለበት። ሰራተኛው በቂ ገቢ(Buying Power) ከሌለው የመግዛት ኃይሉም ደካማ ስለሚሆን በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚመረቱትን ምርቶች ገዝቶ የመጠቀም ኃይል ሊኖረው አይችልም። ካፒታሊስቶችም በተከታታይ ሊያመርቱ የሚችሉትና ቴክኖሎጂዎቻቸውን በየጊዜው የሚያሻሽሉት ቶሎ ቶሎ ምርቶቻቸው ሲሸጡ ብቻ ነው። ይህም ማለት ካፒታሊዝም በተወሰነ የአሰራር ሎጂክ የሚሰራ ሰለሆነ፣ በምርት ክንውን፣ በክፍፍልና በፍጆታ አጠቃቀም(Production, Income Distribution & Conumption) መሀከል ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት መኖር አለበት። ከዚህም ባሻገር የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ከስራ የሚያገኘውን ገቢ የተወሰነውን ባንኮች ውስጥ በቁጠባ መልክ ስለሚያስቀምጡ ባንኮች ኢንቬስት ለሚያደርጉ ካፒታሊስቶች ብድር የመስጠት ዕድል ያገኛሉ ማለት ነው። በዚህ መልክ ወደ መዋዐለ-ነዋይነት የሚለወጠው ገንዘብ ውስጣዊ ኃይል ስለሚያገኝ ለጠቅላላው የገንዘብ ዝውውርም ጥንካሬ በመስጠት የመግዛት አቅሙ ያድጋል። በዚህ መልክ ብቻ ነው አጠቃላይ የሆነ የካፒታሊስት የሀብት ክምችት(Capitalist Accumulation) ሊፈጠርና አገር አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ የሚችለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ስራ ለሚፈልገው ሰው የስራ ዐድል መክፈት የሚቻለው። አብዛኛው ህዝብ የመግዛት አቅሙ ደካማ በሆነበት እንደኛ ባለው አገር ደግሞ ይበልጥ የሚያድገውና የሚስፋፋው ኢንፎርማል ሴክተር ብለን የምንጠራው የተዝረከረከ መስክ ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለዕውነተኛ ህዝባዊ ሀብት ፈጠራ አመቺ አይሆንም። የአገራችን የገንዘብ ምኒስተርና የብሄራዊ ባንኩ ፕሬዚደንት በዚህ መልክ የቀረበውን የካፒታሊዝምን ዕድገትና ውስጣዊ ህግ ቢረዱ ኖሮ ሰላሳ ዓመታት ያህል በተከታታይ የአገራችንን ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ ማድረግ ባላስፈለገ ነበር። 7ኛ) የአንድ አገር መንግስትና አገዛዙ ዋና ሚና በተንኮል ዓለም ውስጥ በመሰማራት ህዝቡን ፍዳውን እንዲያይ ማድረግ ሳይሆን በሳይንሳዊና በፍልስፍናዊ ግንዛቤ አንድ አገርና ህዝብ የሚጠነክሩበትንና የሚያያዙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ስለሆነም ለአንድ አገር መኖርና አለመኖር፣ መጠንከርና አለመጠንከር የኢኮኖሚ ፖሊሲውና በተግባር የሚካሄዱት ነገሮች ወሳኝ ናቸው ማለት ነው። 8ኛ) ይህንን ከተመለከትን በኋላ የአንድ መንግስትና አገዛዝ ሚና ከኢኮኖሚ ግንባታ ባሻገር ዋናው ተግባር ባህል ነክ ነገሮች በሁሉም አቅጣጫ እንዲስፋፉ ማድረግ ነው። በየቦታውም የባህል መስኮችና መንደሮችን በማቋቋም ወጣቱ ትውልድ በትርፍ ጊዜው ወደዚያ በመሄድ እዚያ እንዲሰለጥንና እንዲዝናና ማድረግ ነው። ባህል ፖርኮችን በመስራት የሚወስን ብቻ ሳይሆን፣ ትናንሽና ትላልቅ ቤተ-መጸህፍቶችን ማቋቋም፤ በእንግሊዘኛ የተጻፉ መጽሀፎች በአማርኛ እንዲተረጎሙ በማድረግ ማንኛውም እንደረዳው አድርጎ ማስፋፋት። ከዚህ ውጭ ሙዜየሞችና የቲያትር ቤትችንና ሌሎችን መደጎም የመንግስት ዋናው ተግባር ነው። 9ኛ) ከዚህ በተለየ የአንድ አገር አገዛዝና መንግስት ዋናው ኃላፊነትና ተግባር ብሄራዊ-ነፃነትን ማስከበር ነው። የአንድ ኃያላን መንግስት ተላላኪ በመሆን አገርን ማፈራረስ አይደለም። ስለሆነም የአንድ መንግስትና አገዛዝ ዋናው ተግባር በተለይም የዓለምን ፖለቲካ መረዳትና፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የሚመጣውን ተፅዕኖ በመገንዘብ ብሄራዊ ነፃነትን ማስከበር ነው። የተለያዩ የኢኮኖሚ መመራመሪያ ተቋማትን በየቦታው በማቋቋም ምርምር እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት። በተለይም በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ኢኮኖሚ ከታች ወደ ላይ ኦርጋኒካሊ እንዴት እንዳደገ ምርምር ማድረግና ወጣቱን ማስተማር እጅግ አስፈላጊ ነው። ስለኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክና ሰለኢኮኖሚ ቲዎሪ በቂ ዕውቀት ሲኖር ብቻ ነው ስለካፒታሊዝም ዕድገት መረዳት የሚቻለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ከውጭ የሚመጣውን ግፊት መቋቋምና ኤክስፐርት ነን የሚሉትን ተንኮል ወይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መረዳት የሚቻለው። በተቻለ መጠን በውጭ ኃይሎች ወይም ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ አለመመከር ነው። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገቡትን ሰላዮች በቅጡ መከታተለና ማጥናት ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ካለአግባብ ትላልቅ ቦታ እየተሰጣቸው ትላልቅ የኤምባሲ ግቢዎች እንዲሰሩ የተደረጉት ወደፊት ሁኔታው የሚስተካከልበት መንገድ መፈለግ። አገዛዞችን የሚቆጣጠር የውጭ ኃይል ካለና ረባሽ ኃይሎችን የሚመለመሉ ከሆን አንድ መንግስትና አገዛዝ በነፃ አገራቸውን መገንባት በፍጹም አይችሉም። ስለአገርና ስለብሄራዊ ነፃነት በምናወራበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በቅጡ ማሰብ አለብን። 10ኛ) ከዚህ ወጣ ስንል የአንድ አገዛዝ ዋናው ተግባርና ኃላፊነት ህዝቡ መብቱ የሚከበርበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ካለምንም ወንጀል በፖሊሶች እንዳይጎሳቆል ማድረግ፣ ወንጀል ከፈጸመም በህግ የሚጠየቅበትን ሁኔታ መፍጠር። ይህም ማለት ፖሊስ ካለአግባብ በወገኖች ላይ በደል እንዳይፈጽም አስፈላጊውን ትምህርትና የሳይኮሎጂ ስልጠና እንዲያገኝ ማድረግ። ህግን የሚጥስና ግለሰእቦችን የሚያጎሳቁል ፖሊስ በህግ መቀጣትና ከስራው መባረር አለበት። 11ኛ) ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የአንድ አገዛዝና መንግስት ዋናው ተግባር በአገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍኑ ማድረግ ነው። ሰላምና ፀጥታ በሌለበት አገር ውስጥ ደግሞ በአገራችን አጠራር ልማት የሚባለው፣ በሳይንሱ ደግሞ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ሊኖር በፍጹም አይችልም። የአንድ መንግስትና አገዛዝም ዋናው ተግባር ህዝቡ ስቃዩን እንዲቀንስና የመንፈስ ደስታ እንዲሰማው አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው መንግስት የሚባለውና አገዛዙ ህዝቡ የሚፈልገውንና የሚጠብቀውን ኃላፊነት ሊወጡ የሚችሉት። መንግስትና አገዛዝ ራሳቸውን እንደገዢዎችና አዛዞች የሚቆጥሩ ሳይሆን አገልጋዮች መሆናቸውን መረዳት አለባቸው። ለዚህም ነው ህዝብ ቀረጥ የሚከፍለውና የሚመግባቸው። ቀረጥ የሚከፍልና ምግብ የሚያቀርብ ህዝብ ደግሞ በቂና የሰለጠነ አገልግሎት እንዲሰጠው ያስፈልጋል።
ሌሎች አንድን መንግስትና አገዛዝ እንደ አገዛዝ የሚያስጠሩትን ነገሮች ትተን ከላይ በተዘረዘሩት ነገሮች ላይ ብቻ ብናተኮር የዛሬው የአቢይ አህመድ አገዛዝ አንዳቸውንም ቅደመ-ሁኒታ የሚያሟላ አይደለም። ስልጣን ይዞ ትንሽ ከተንገዳገደ በኋላ ባለፉት አራት ዐመታት የሚያካሄደው ፖለቲካ ፖለቲካ የሚባል ሳይሆን ህዝብን ማደናበርና አገራችንን ማመሰቃሰል ነው። ህዝባችን ሰላም እንዲያጣ በማድረግ እፎይ ብሎ እንዳይኖር ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግስታዊ ድጋፍ ያላቸው ሸኔ የሚባሉና ቄሮዎች በመታጠቅና በመዘዋወር ከፍተኛ ጭፍጨፋ እያካሄዱ ነው። በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር ፋሺሽታዊና የአፕርታይድ አገዛዝ ሰፍኗል ማለት ይቻላል። ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የአፍሪካ አህጉር አደገኛ የሆነ አገዛዝ ተንሰራፍቷል። እነረዋንዳ የመሳሰሉት በካጋሜ የሚገዙት፣ ብዙ ጭፍጨፋ የተካሄደባቸው አገሮች ህዝቡ በሰላም የሚኖርባቸውና ስቃይን ያየውና ዘመዶቹና ጓደኞች የሞቱበት ህዝብ የስነ-ልቦና ስልጠናና ድጋፍ ይሰጠዋል። በአንፃሩ የሰላም ኖቭል ተሸላሚ በሆነው በአቢይ አህመድ በምትተዳደረው አገር በተለይም አማራው በማንነቱ ከቀየው ይፈናቀላል፤ ይገደላልም። አቢይ ከወያኔዎች ጋር በመናበብና በመተባበር በአማራው ላይ የመጨረሻውን ፍልሚያ(The Final Solution) ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። ይህ ብቻ ሳይሆን የአቢይ አገዛዝ ለትግራይ በጀት ሲመደብ የወልቃይት ጠገዴ አስተዳደር በጀት አይመደብለትም። እንዲያውም መሬቱን ለወያኔ እንዲሰጥ አቢይ አህመድና አገዛዙ ሽር ጉድ እያሉ ነው። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው አቢይ በተለይ አማራን፣ በአጠቃላይ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደሚጠላ ነው። አገር እያፈራረስና ህዝብን እያፈናቀለ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ኢትዮጵያ በምንም አትፈርስም እያለ ህዝቡን ያታልላል። በአጠቃላይ ሲታይ የሰውየውና በአካባቢው የተሰበሰቡት፣ እንዲሁም የኦሮምያና የአማራው ክልል አገዛዞች ዋናው ተግባራቸው ተንኮል መጠንሰስና በህዝብ ላይ ጦርነት ማወጅ ሆኗል። የአገዛዙም ዋና የፖለቲካ ፍልስፍና ዱሩዬነት፣ ተንኮልና ሽወዳ፣ ከዚህም በላይ አመጽ ለመሆን በቅቷል። ይህ ዐይነቱ አካሄድም ከሞላ ጎደል ተቀባይነትም በማግኘት፣ በተለይም የንዑስ ከበርቴው መደብና ምሁር ነኝ ባዩ በዚህ ዐይነቱ አገርን የማፈራረስ ስትራቴጂ ውስጥ በመሰማራት ዋናው ተግባራቸው ህዝብን ማታለልና የአገዛዙን ዕድሜ ማራዘም ሆኗል ማለት ይችላል።
ባጭሩ በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ ሌላው ቢቀር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ወደ ኋላ-የቀረ ነው። እንደ ጋምቢያ የመሳሰሉ አገሮች እንኳ ሲከበሩ አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ አገራችንና ህዝባችንን አስንቀዋል። በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ በአገሩና በህዝቡ ላይ ወንጀል ከፈጸመ እንደወያኔ ከመሰለ የወንበዴ ቡድን ጋር በመቀመጥ ይደራደራል። በዚህ ዐይነት የማጭበርበር ስልት አሁንም በተደጋጋሚ የአማራው ክልል በጦርነት ወጥመድ ውስጥ እንዲገባ ሁኔታውን እያመቻቸ ነው። ስለሆነም ይህን ዐይነት ወንጀል በተደጋጋሚ የሚፈጽም አገዛዝ በስልጣን ላይ የመቆየት መብት የለውም። በተለይም ወያኔን የስልጣን ተቋዳሽ እንዲሆንና አብሮ ኢንዲገዛ ለማድረግ አመቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ከዚህም በላይ የአማራውን መሬት የሆነውን የወልቃይት ጠገዴንና የራያን መሬት ቆርሶ ለወያኔ ለመስጠት መሞከርና በአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖዎች ላይ ጦርነት ማወጅ የአቢይን አዕምሮ-ቢስነት ነው የሚያሳየን። ከዚህም በላይ የወልቃይት ጠገዴና የራያ መሬት ለወያኔ የሚሰጥ ከሆነ በአካባቢው ሰላም እንዳይፈጠር ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የጥሬ-ሀብት ዘራፊዎች የሆኑት ትላልቅ የአሜሪካ ኩባንያዎች ጥሬ-ሀብትን በማውጣት ከፍተኛ ማህበራዊና እኮሎጂያዊ ቀውስ ለመፍጠር አመቺ ሁኔታን ያገኛሉ። በደቡብ አፍሪካም የተካሄደው የሰላም ስምምነት የሚባለው አንደኛው ዓላማው ኢትዮጵያን የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ማድረግና አገራችንን በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መክተት ነው። ባጭሩ አቢይ ከወያኔ ጋር በማበር በህዝባችን ላይ የሚፈጽመው ወንጀል በአስቸኳይ መቆም አለበት። አቢይ የሚባል ጭንቅላቱ በተንኮል የተመረዘ ሰውና፣ ወያኔ የሚባለው እንዲሁም በጥላቻ መንፈስና በበላይነት ስሜት የተበከለው ኃይል እስካሉ ድረስ በአገራችን ምድር ሰላም አይሰፍንም። እነዚህ ኃይሎች የታሪክና የባህል ንቃተ-ህሊና ስለሌላቸው ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የሚመለሱ አይደሉም። ስለሆነም የኦሮሞ ኤሊትና ወያኔዎች በመተባበር አገራችንን ለማዳከምና ህዝባችንን ለመበታተን የሚሸርቡትን ሴራ በተባበረ ክንድ መቀልበስ አለብን። መልካም ግንዛቤ!!
https://www.youtube.com/watch?v=NLoSQuxBtiU
ማሳሰቢያ፣ አንድን አገር አማቱሪዝም በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ መምራት በፍጹም አይቻልም። ለህዝብና ለአገር መቆም የግዴታ በቂ ዕውቀትንና የሞራል ብቃትነትን ይጠይቃል። እስካሁን በተጓዝንበት መንገድ ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ማለት ዘበት ነው። ስለሆነም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሳተፉበትና አብዛኛውን ጊዜያቸውን ፕሮፌሽናል በሆነ መልክ ሲያውሉ ብቻ ነው አንድን አገር በተሟላ መልክ ማሳደግና ህዝብንና አገርን ማስከበር የሚቻለው። ሌላው በመሀከላችን ያለው ትልቁ ችግር አብዛኛዎቻችን ለዕውቀት ኢንቬስት ማድረግ አንፈልግም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የተጻፉ መጽሀፎች ብዙ ወጪ ከወጣባቸው በኋላ ተቀመጥዋል። ይህ በራሱ ደግሞ ለአገርና ለህብረተሰብ የሚጠቅሙ ሳይንሳዊ መጽሀፎችን በተከታታይ እንዳይጻፍ ያግዳል፤ ሀሞት ያፈሳል? ታዲያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ትችታዊና ለዕድገት የሚጠቅሙ መጽሀፎችን እንዴት መጻፍ ይቻላል?
Literature:
BoP Jessop; The Capitalist State, Great Britain, 1982
Nicos Poulantzas; The Theory of the State: Political Structure,
Ideology and Socialist Democracy, Paris, 1977
Otto Apelt; Plato: The State, Hamburg, 2004