Becoming the member of the WTO has no any economic advantage for an underdeveloped Economy!
የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን
ፋይዳ-ቢስነት !!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
01.1.2019
መግቢያ
ከዚህ ቀደም ባወጣኋቸው ሁለት ጽሁፎቼ፣ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት(WTO)አባል ብትሆን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንና እንደ ህብረተሰብም ልትገነባ እንደማትችል በቲዎሪም ሆነ በተግባር(empirical) ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በተጨማሪም፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባወጣሁት ጽሁፌ፣ አገዛዙ ተገዶም ሆነ ፈቅዶ በዓለም ባንክና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም (Structural Adjustment Program) ተግባራዊ በማድረጉ በነጻ ገበያ ስም የተካሄደው ፖሊሲ የአገራችንን ኢኮኖሚ ወደ ፊት እንዳላረመደው ለማረጋገጥ ሞክሬያለሁ። በነጻ ገበያ ፖሊሲ የተነሳ ወደ ውስጥ ያተኮረና ጠቅላላውን ህብረተሰብ ያካተተ ኢኮኖሚ የተገነባ ሳይሆን፣ ጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል የጠቀመና አባዛኛውን ደግሞ ወደ ድህነት የገፈተረ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ተዘርግቶ ህብረተሰብአዊ ትርምስ እንደተፈጠረ ከጽሁፉ መገንዘብ ይቻላል።
ኢትየጵያ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ያመለከተችው እ.አ በ2003 ዓ.ም ቢሆንም፣ ውይይቱ የተጀመረው ከሁለት ዐመት በፊት ነው። ውይይቱም የሚካሄደው በቀጥታ ከንግድ ድርጅቱ ጋር ሳይሆን፣ የንግድ ድርጅቱ ይወክሉኛል በሚላቸው አገሮችና እሱ „መርጦ“ ባስቀመጣቸው ከነ ሰሜን አማሪካ፣ ከአውሮፓው አንድነትና ከአንዳንድ አባል አገሮች ጋር ነው። እንደሚታወቀው አንድ አገር የድርጅቱ አባል ሆና ከመግባቷ በፊት ብዙ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ የቀድሞው የድርጅቱ ጸሀፊ የነበሩት ሚስተር ማይክ ሙር በትክክል እንደሚሉት፣ አባል ለመሆን ያመለከተው መንግስት ጥቅሙንና ጉዳቱን በሚመለከት ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር፣ ለምሳሌ እንደ ገበሬ ማህበር፣ የሰራተኛው ማህበር፣ የንግድና የኢንዱስትሪ መስክ ተጠሪዎችና እንዲሁም የተለያየ አመለካከት ካላቸው ምሁራን ጋር ሰፊ ውይይት ማካሄድ እንደሚያሰፈልግ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታተም ካፒታል ለተባለ መጽሄት ላይ በህዳር ወር 2009 ዓ.ም በተደረገ ቃለ-መጠይቅና መልስ አብራርተዋል። በመቀጠልም የቀድሞው ጸሀፊ የነበሩት ሚስተር ሙር ሲያብራሩ፣ ውይይቱ ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደማይቸልና፣ አንድ አገርም አባል ከመሆኗ በፊት ብዙ ጥናት ማካሄድ እንዳለባትና፣ ጥቅም ማግኘቷንና አለማግኘቷን በበቂው ማውጣትና ማውረድ እንዳለባት ያሳስባሉ። ለምሳሌ ቻይና ካመለከተች በኋላ አስራአምስት ዐመት ያህል መጠበቅ እንደነበረባት ያመለክታሉ። የኢህአዴግ መንግስት የድርጅቱ አባል ለመሆን ከሰባት ዐመት በፊት ያመለከተ ቢሆንም ውይይቱ የተጀመረው በ2008 ዓ.ም ነው። ይሁንና የኢህአዴግ መንግስትና የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ የንግድ ምኒስተር የሆኑት ኢትዮጵያ ቶሎ አባል መሆን አለባት እያሉ በመጎትጎትና የሲቪክ ማህበረሰቡን ሳያማክሩ ጥድፊያውን ተያይዘውታል።
ይህንን አስመልክቶ አንድ ሰሞን ከሰሜን አሜሪካን ልዑካን የመጡ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም የድርጅቱ አባል ለመሆን ጥቅምነቱን በሚመለከት በአቶ ወንድወሰን ሸዋረጋና በአቶ አበበ አበባየሁ በወርክ ሾፕ አማካይነት ማብራሪያ ተሰጥቷል። በእነሱ አገላለጽም የድርጅቱ አባል መሆን ፋይዳ እንዳለውና፣ ድርጅቱ በተለይም ያልበለጸጉ አገሮች ጠበቃ በመሆን በአባል አገሮች መሀከል ምርቶቻቸውን እንዲያራግፉ ያመቻቻል ፤ ከፍተኛ ጥቅምም ያገኛሉ ይሉናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና ከተደራጁ ምሁራንና የሶስተኛው ዓለም አገሮች ጠበቃዎች ከሆኑት የሚሰማውና የሚቀርበው ጥናት ግን አነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን ምሁራን ከሰጡት ሀተታ ጋር በፍጹም የሚስማማ አይደለም። የኒዎ-ሊበራልን አጀንዳ ከሚቃወሙ ኃይሎች የሚሰማው፣ ልክ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ የንግድ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነጸ ንግድን የሚያስፋፋ ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃም በሎቢይስቶች የተሰገሰገ ለመሆኑ በሚገባ ያብራራሉ። በመቀጠልም፣ ደካማ አገሮች የዚህ ዐይነት ድርጅት አባል ከሆኑ ወደ ውስጥ የሰከነና ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ እንደማይችሉ በሰፊው ያስረዳሉ። የንግድ ድርጅቱ የተቋቋመው እ.አ በ1947 ዓ.ቢሆንም፣ ይበልጥ መስፋፋት የጀመረው የኒዎ-ሊበራል አጀንዳ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ካገኘና አማራጭም የሌለው ሆኖ መቅረብ ከጀመረ ወዲህ ነው። እ.አ በ1995 ዓ.ም ድርጅቱ ስሙን ወደ ዓለም የንግድ ድርጅትነት ከለወጠ በኋላና እንደ ዕድገት የመሳሰሉትን አጀንዳዎች ካካተተ ወዲሀ ብዙ አገሮች ጥቅም እናገኛለን በማለት አባል ለመሆን አመልክተዋል። ይሁንና ግን ጠንክረው ከወጡ እንደቻይና ከመሳሰሉት አገሮች በስተቀር ሌሎች ደካማ አገሮች የዕቃ ማራገፊያ ከመሆን አላለፉም።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አባል የመሆን ዕድል ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፍ በገበያ ህግ መሰረት ማንቀሳቀስ እንዳለባትና፣ ኢኮኖሚው ለውጭ ንግድ ልቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አንደ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ቴሌኮሙኒኬሽን የመሳሰሉት በሙሉ ሊበራላይዝ መሆን አለባቸው ወይም ከመንግስት መዳፍ መላቀቅ አለባቸው እያሉ እየጎተጎቱ ነው። ይህንን በሚመለከት ከብዙ የሊበራል ኢኮኖሚን አጀንዳ እናራምዳለን ከሚሉ ኢትዮጵያውያን፣ ይሁንና ደግሞ የኢሀአዴግን አገዛዝ ከሚቃወሙ ድርጅቶች የሚሰማው ሮሮ መንግስት ሙሉ በሙሉ የንግድ ድርጅቱንም ሆነ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ የሚሉትን የፊናንስ መስኩን ሊበራላይዝ አላደርግም ማለቱ ትክክል እንዳይደለ ነው። እዚህ ላይ ርስ በርሳቸው የሚጋጩ አቋሞች አሏቸው ማለት ነው። ይህንን ለጊዜውም ትተን ወደ ድርጅቱ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ጠበቃነት ስንመጣ ብዙ ውይይቶችና ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት የንግድ ድርጅቱ በምንም ዐይነት የደካማ አገሮች ጠበቃ እንዳለሆነ ማረጋገጥ ይቻላል።
ግልጽ ያልሆነና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አወቃቀር !
የዓለም ንግድ ድርጅት ከአንድ አገር ወይም ደግሞ ከጥቂት አገሮች ጥቅም አንጻር የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን 1ኛ) ላይ እንደተዘረዘረው ደርጅቱ የሚመራበት ፍልስፍና ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ስልጣኔ ነው፤ 2ኛ) አወቃቀሩም ሆነ አሰራሩ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ነው። የመጀመሪው አንድን ቲዎሪንና የአሰራር ዘዴን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ የተለያዩ ችግሮችንና መነሻቸው ልዩ የሆነውን በአንድ ዐይነትና ተመሳሳይ መንገድ ሊፈታ ይቃጣል። እንደሚታወቀው አንድ የዓለምን ህዝብ የሚያስማማ ጉዳይ አለ። ይኸውም ማንኛውም ህዝብ ሆነ ህብረተሰብ የግዴታ ማምረት፣ ልውውጥና ክፍፍል ( production,exchange and distribution) ማድረግ አለበት። 2ኛ) የሰዎች ፍላጎት እንዲሟላ ከተፈለገ በአንድ አገር ውስጥ የግዴታ የስራ ክፍፍል መዳበር አለበት። ይህ ሁኔታ የግዴታ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ያመራናል ማለት ነው። ወደ ንጹህ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ስርዓት ያምራ አያምራ በብዙ ነገሮች ነው ሊወሰን የሚችለው። እስከዚህ ድረስ መስማማት ካለ፣ በሌላ ወገን ግን አሜሪካን አገር የሰፈነው ወይም ደግሞ እንግሊዝ የተጓዘችበትን መንገድ ለሌላውም ማገልገል ይችላል የሚል የተፈጥሮ ህግ የለም። አንዳንድ ትምህርቶችን ግን መቅሰም ይቻላል። ይሁንና እንደ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባይሎጂ የመሳሰሉት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ቢኖራቸውም፣ ኢኮኖሚክስ የተፈጥሮ ሳይንሰ እንዳለመሆኑ መጠን ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊኖረው አይችልም። የየአገሮች ባህል፣ ታሪክና የአኗኗር ስልቶች እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ መጠበቅ ስላለባቸውና፣ ራሳቸውም ራሳቸውን ስለሚከላከሉ የሌላን አገር አሰራርና አበላል አምጥቶ አንድ አገር ውስጥ ልትከል ቢሉት የባህል ቀውስ ይፈጥራል። ካለብዙም ውጣ ውረድ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በሶስተኛው ዓለም አገሮች በልዩ ልዩ ስም ተግባራዊ የሆኑትን፣ በመሰረቱ የነጻ ንግድ ፖሊሲዎች ስንመለከት፣ ጥሩ ውጤት ማምጣት ያልቻሉት የየአገሮችን ባህል፣ ስነ-ልቦናና የማቴሪያል ሁኔታዎች በሚገባ ለመገምገምም ሆነ ለመረዳት ባለመቻልና ባውቃለሁ ባይነት እንዲቀበሉት በማድረግ ነው። በዚህም ምክንያት የፍጆታ አጠቃቀሞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ልማዶች በመወሰዳቸው የአስተሳሰብ መዘበራረቅንና የባህልን መበላሸት ሊያስከትል ችሏል። በአገሮች መሀከል የግዴታ የንግድ ግኑኝነት መኖር ያለበት ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ግን አንድ አገር የዚህ ወይም የዚያኛው ኢኮኖሚያዊም ሆነ የንግድ ድርጅት አባል መሆን አያስፈልጋትም። የለም የግዴታ አባል መሆን አለባት ከተባለ ደግሞ የሚያመጣውን ጥቅምና ጉዳት በሚገባ መገምገም የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ብዙ ልፋትንና ወጪን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን አገዛዙም ሆነ ኤሊቱ በሆነው ባልሆነው ነገር በመነታኮር ዕውነተኛውን የዕድገት ፈለግ እንዳይዙና ተጨባጭ ስራ እንዳይሰሩ ይታገዳሉ። ይህም ፀሀፊ በዚህ ዐይነቱ ለምንም የማይጠቅምና ሳንሳዊ ይዘት በሌለው ነገር ላይ መረባረብ ባላስፈለገው ነበር።
ዛሬ የዓለም ንግድ ድርጅት ተብሎ እንዲጠራና ተግባሩም ከንግድና ንግድን ከመሳሰሉ ነገሮች አልፎ ዕድገትን፣ የአካባቢ ቀውስን እንዲሁም ሌሎች ለዕድገት ይጠቅማሉ ብሎ የታሰቡትን ያካተተ ቢሆንም፣ እንደ ታሰበውና ስምምነት እንደተደረሰበት ብዙ ነገሮች ተግባራዊ መሆን አልቻሉም። እ.አ በ1995 ዓ.ም ድርጅቱ ስሙን ለውጦ የዓለም ንግድ ድርጅት ተብሎ እንዲጠራና በመግቢያውም ላይ ጤናማና ለተስተካከለ ዕድገት(Sustainable development) ጠበቃ ሆናለሁ ቢልም እስካሁን በተግባር እንደታየው የተቃራኒው ነው እየሆነ የመጣው። በሌላ አነጋገር ጤናማ ዕድገትና የአካባቢን እንክብካቤ የሚመለከት ክንውን ተግባራዊ ሲሆን በፍጹም 㜎አይታየም። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ?
የንግድ ድርጀቱ ወደ 153 የሚጠጉ አባል አገሮች ቢኖሩትም የድርጅቱን ህልውና የሚወስኑ ሁለት አህጉሮችና ሁለት አገሮች ናቸው። እነዚህም ሰሜን አሜሪካ፣ የአውሮፓ አንድነት፣ ጃፓንና ካናዳ ናቸው። ከ70% በላይ የሚሆነው ንግድም ሆነ የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ(FDI= Foreign direct investment) በእነዚህ አገሮች መሀከል የሚካሄድ ነው። እነዚህ አገሮች ከብዙ መቶ ዐመታት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአሰራር ስልትና ህግን ስላዳበሩ በቀላሉ ሌሎች ደካማ አገሮችን ሊያታልሉበት የሚችሉባቸው መሳሪያዎች አላቸው ማለት ነው። በዚህም ምክንያት እነዚህ ሁለት አህጉሮችና ሁለት አገሮች አንድ ድርጅቱን የሚመለከት ስብሰባ ከመደረጉ በፊት ርስ በራሳቸው በመገናኘት ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በዚህም ምክንያት ይህንን የደረሱበትን ስምምነት በሁሉ አባል አገሮች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የተወሰኑ አገሮችን በቡድን ቡድን እየመረጡ ያነጋግራሉ። በዚህ መልክ አንድ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት በትናንሽ አገሮች ላይ ግፊት ያደርጋሉ። የሶስተኛው ዓለም አገሮች በድርጅቱ ውስጥ በቁጥር ከፍተኛውን ቦታ ቢይዙም ዋና ወሳኞቹ እነዚህ ጥቂት የኢንዱስትሪ አገሮች ናቸው።
ይህ ሁኔታ የመነጨው ራሱ ድርጅቱ ባለው ውስጣዊ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አወቃቀር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወሳኞቹ የሚኒስተሮች ጉባዬ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ በህገ-ደንቡ ላይ ያልሰፈረ የዝቅተኛ ሚኒሰተሮች ጉባኤና በድርጅቱ የተመረጡ አገሮች ጥቂት ተጠሪዎች የሚወስኑት የመነጋገሪያና መጨረሻም የመስማሚያ ነጥብ ይሆናል ማለት ነው። ይህን አስራር አስመልክቶ የአሁኑ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ሚስተር ላሚ በ1999ና 2003 ዓ.ም በሰጡት ማብራሪያ የንግድ ድርጀቱ የማዕከለኛውን ዘመን የመሰለ ወደ ኋላ የቀረ አዋቃቀርና አሰራር እንዳለው በግልጽ ተናግረዋል። ስለሆነም የዜና ማሰራጫ ወኪሎችም ሆኑ የሲቪሉ ማህበረሰብ የዓለም ንግድ ድርጅቱ የቀን ተቀን በሚያካሂደው ስራና የምኒስተሮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው ሁኔታውን የማዳመጥና የመገምገም መብት የላቸውም። ይህም ማለት ውይይቱና ለአጀንዳ የሚቀርቡት ነጥቦች በተዘጋ ችሎት የሚወሰኑ ናቸው ማለት ነው። ግልጽነት የሌለው አሰራር ነው ማለት ነው።
ከዚህ ስንነሳ የንግድ ድርጅቱን ስምምነትና ህግ የሚጥሱ አገሮች የሚቀጡት በእነዚህ ጥቂት ኢንዱስትሪ አገሮች ቀድሞውኑ በተደነገገ ህግ መሰረት ነው። ዳኛውም ከሳሹም አንድ ናቸው። በዚህም ምክንያት አንዳንድ አገሮች የድርጅቱን የንግድ ስምምነት ሲጥሱ፣ ወይም ደግሞ በሁለት አገሮች መሀከል ከንግድ ጋር የተያያዘ ጠብ ሲፈጠር ደርጅቱ በሚያዘጋጀው አስታረቂ ኮሚቴ ጥብቅ በሆነ የአሰራር ዘዴ መፈታት አለበት። ውሳኔ የተጣለበት አገር በጥብቅ የዳኞችን ቅጣት በተግባር ማዋል አለበት ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነቱን ቅጣት የኢንድስትሪ አገሮች መቋቋም ቢችሉም የሶስተኛው ዓለም አገሮች ግን በፍጹም ሊቋቋሙት አይቸሉም። አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ዐይነቱ ፍርድና ውሳኔ የኢንዱስትሪ አገሮችን የሚጠቀም ነው ማለት ነው።
እስካሁን ድረስ ያለው ልምድ እንደሚያረጋግጠው የንግድ ውይይቱ በተራ ነጋዴዎች መሀከል የሚደረግ ዐይነት ነው የሚመስለው። ይህንን ከሰጠኸኝ ያንን እሰጥሀለሁ የሚመስል ዐይነት ውይይት። አብዛኛውን የንግድ ስምምነቶች የተካሄዱት እ.አ በ1986-1994 የኡራጋይ ዙሪያ ተብሎ በሚታወቀው ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የተደረጉትና የሚደረጉት ውይይቶችና የተደረሰባቸው ስምምነቶች ይህንን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ሁሉም አባል አገሮች ስምምነቶቹን በግዴታ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው። በየንግድ ድርድሮች ላይ ሌሎች እርእስቶችም በተከታታይ ይካሄዳሉ። ይሁንና የንግድ ስምምነቱም ሆነ ሌሎችም ነጥቦች በአንድ ቀን ይደመደማሉ። እንደዚህ ዐይነቱ ውይይትና የተለያዩ ነጥቦችን አንስቶ ወደ ስምምነት ለመድረስ መጣደፍ ልምድ የሌላቸውን አገሮች መጉዳቱ ብቻ ሳይሆን ደካማ አገሮች ጥቂት ጥቅም አገኘን ብለው ሊወጡ የማይችሉት ስምምነት ውስጥ እንዲገቡ ይገደዳሉ ማለት።
በንግድ ድርጅቱ ህግና ስምምነት መሰረት የአመራረት፣ የአጠቃቀምና በአጠቃላይ ደግሞ የአካባቢን እንክብካቢ የሚመለከቱ ጉዳዮች ይጣሳሉ። የየአባል አገሮች የስራ ሁኔታና የአከፋፈል ጉዳይ በድርጅቱ ደንብ ውስጥ የተካተቱ አይደሉም። ዋናው ነገር ምርትን አምርቶ በዓለም ገበያ ላይ ማራገፍ ነው። ለምሳሌ የሚመረቱት ምርቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ የሚራገፉት ከንጹህ ነጻ ንግድ አንጻር እንጂ ለሰው ጤንንት ይስማሙ አይስማሙ፣ በምርቶች ውስጥ ያሉት ጤንነትን የሚያቃውሱ ኬሚካሎችና አካባቢን የሚመርዙ ማዳበሪያና የተባይ ማጥፊያ በድርጀቱ እስከዚህም ክትትል የሚረግባቸው አይደሉም። በድርጅቱ አባሎች መሀከል የሚደረጉት የምርት ልውውጦች በእኩልነት የሚታዩ ናቸው። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ምርት በዝቅተኛ ደረጃ መታየት የለበትም። ለምሳሌ አንድ አገር የድርጅቱ አባል ከሆነች የአውሮፓ ወይም የአሜሪካ ስጋ ለህዝቤ ጤንነት ሊስማማ አይችልም ብላ እምቢ ልትል አትችልም። በዚህም ምክንያት ለአገፘ ህዝብ የማይጠቅምንና ጤንነትን የሚያቃውሱ ምርቶች በእኩልነት(non-discriminatory) መታየት አለባቸው በሚል የማያስፈልጋትን ምርት ወደ አገፘ እንድታስገባ ትገደዳለች። አንድ አገር ለህዝቧ በቂ ስጋ ወይም እህል ማምረት ብትችልምና የተከማቸ ቢኖራትም አባል ከሆነች የግዴታ ማስገባት አለባት ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ለምሳሌ በጥራታቸው ጥሩ የሆኑ የኦርጋኒክ ምርቶች በኬሚካል ማዳበሪያ ከተመረቱት በላይ ሆነው መታየት የለባቸውም። ለምሳሌ በንግድ ድርጅቱ ደንብ መሰረት ኦርጋኒክ ምርቶች ናቸው፤ ለጤንነት ይስማማሉ ተብሎ በማሸጊያዎች ላይ መጻፍ ወይም ምልክት መደረግ የለበትም። በንግድ ድርጅቱ ህግ መሰረት እንደዚህ ዐይነቱ አሰራር የነጻ ንግድን እንቅስቃሴ ያግዳል። በዚህም ምክንያት የተፈጥሮን ህግና የአካባቢን መጠበቅ የሚያስቀድሙና ለሰው ልጅ ጤንነት የሚስማሙ የአስተራረስና የአመራረት ዘዴዎች በንግድ ድርጅቱ ቦታ አይሰጣቸውም። ምክንያቱም ለየት ያለ አስተራረስና የዘር አጠቃቀም የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ጥቅም ስለሚጻረር ነው። ሁሉም አባል አገር እንደፈለገው አምርቶ በዓለም ገበያ ላይ ማራገፍ ይችላል ማለት ነው። በዚህ ዐይነት㜎የነጻ ንግድ ስምምነት ላይ የተመሰረተ የአመራረት ዘዴ በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ቀውስና ቀውሱን ለማስወገድ የሚወጣው ወጪና በመጭው ትውልድ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባ አይደለም ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የንግድ ድርጅቱ ስምምነትና ደንብ እ.አ በ1992 ዓ.ም በሪዮ በብራዚል የተደረገውን የዓለም ማህብረሰብ ጤናማ የአመራረት ዘዴና የአካባቢን እንክብካቤ መጠበቅ አለበት የሚለውን ደንብ የሚጥስ ነው። ስለሆነም የኢንዱስትሪ አገሮች በአካባቢ ላይ ጉዳት ለሚያደርሱ ለትላልቅ አራሽ ገበሬዎች ያሚያደርጉትን ድጎማ የንግድ ድርጅቱ ምንም ዐይነት ተቃውሞ አያሳይም። እንደሚታወቀው ማንኛውም የመንግስት ድጎማ የነጻ ገበያን የሚጻረር ሲሆን የንግድ ድርጀቱ ግን እርስ በርሱ የሚቃረን ፖሊሲ ያካሂዳል። በዚህም ምክንያት የነጻ ንግድ ስምምነት ከጤንነትና ከአካባቢ መናጋት በላይ የሚታይ ነው።
በአለፉት አስር ዐመታት የንግድ ድርጅቱ ማድረግ ከሚገባው በላይ ብዙ ነገሮችን በደንቡ ውስጥ እያካተተና ውስብስብ እያደረገ የመጣ ነው። ለምሳሌ የመዋዕለ-ነዋይ(investment) ጉዳይ በንግድ ድርጅቱ ደንብ ውስጥ መካተት እንደሌለበት ተከራካሪዎች አጥብቀው ያነሳሉ። የንግድ ድርጅቱ አባል አገሮች የፓቴንት ስይስተም ማስገባት አለባቸው። ይህ ዐይነቱ የፓቴንት ወይም ፈቃድ አትክልቶችንና ሌሎች ጠቃሚ አፅዋትን፣ እንስሶችንና የሰውንም ጂን ይመለከታል። በዚህም መሰረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸው የኢንዱስትሪ አገሮች አንድ ደካማ አባል አገር ሄደው በምርምርም ሆነ በአጋጣሚ አንድ ነገር ካገኙ ይህንን ለራሳቸው ፓቴንት ማድረግ ይችላሉ። ይህም ቀጥተኛ ዘረፋን( Bio piratery) ያስከትላል።
የመጨረሻም በጉልህ እንደሚታወቀው፣ የንግድ ድርጅቱ የምዕራብ አውሮፓና የአሜሪካን እንዲሁም የጃፓንን ትላልቅ ኩባንያዎች ጥቅም የሚያራምድና በነሱ ቁጥጥር ስር የወደቀ ነው። አብዛኛው ውሳኔዎችም በትላልቅ ኩባንያዎችና በድርጅቱ የተዘጋ ችሎች የሚደነገጉና ሌሎች ደካማ አገሮች እንዲቀበሉት የሚደረግ ነው። ስለዚህም እንደ ኢትዮጵያ የመሰለች ደካማ አገር የእነዚህ ኩባንያዎች መጨፈሪያ ከመሆን በስተቀር ለዕድገቷ የሚሆን ጥቅም በፍጹም ልታገኝ አትችልም።
በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ !
አንድ አገር እንደዚህ ዐይነት የንግድ ስምምነት ውስጥ ስትገባ በዚህ አማካይነት ብዙ አምርቼ በአባል አገሮች ገበያ ላይ በማራገፍ ለውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር እችላለሁ ብላ በመገመት ነው። ምርቷን በዓለም ገበያ ላይ ስትሸጥ፣ የውጭ ካረንሲ በማግኘት 1ኛ) ራሷ ማምረት የማትችለውን የፍጆታ ዕቃ ገዝታ በማስገባት ገዝቶ ለመጠቀም ለሚችለው ገበያ ላይ ለማቅረብ፣ 2ኛ) የምርት ማምረቻዎችንና ሌሎች የረዥም ዕድሜ ያላቸውን ዕቃዎች በማሰገባት ኢኮኖሚውን በማደረጃት የውስጥ ገበያዋን ለማዳበር ነው። ለዚህ ደግሞ በዓለም ገበያ ላይ የምታቀርበው ምርት ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ለምሳሌ ብዙ አባል አገሮች ተመሳሳይ ምርት የሚያመርቱ ከሆነ ገበያው ከሚችለው በላይ ስለሚሆን እንደልቧ ብዙ ምርት አራግፋ በቂ የውጪ ከረንሲ ልታገኝ አትችልም። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች አብዛኛውን ጊዜ የእርሻና ከእርሻ ጋር የተያያዙ የምርት ውጤቶች ናቸው። ምርቶቹ ደግሞ በጥሬ መልክ ስለሚቀርቡ ተሸጠው የሚያስግቡት ገቢ ለዕድገት የሚያመጡት ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያለፈው ስድሳ ዐመት ልምድ እንደሚያረጋግጠው በተሳሳተ የኢኮኖሚ ፍልስፍናና ፖሊሲ በመመራቷ፣ በአንድ በኩል ወደ ውጭ የምትልከው የምርት መጠን ሊያድግ አልቻልም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ወደ ውስጥ ኢኮኖሚው በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ለህዝቡ የስራ መስክ በሰፊው መክፈት አልተቻለም። የንግድ ድርጅቱ አባል የመሆን ዕድል ብታገኝ ይህ ሁኔታ ሊሻሻል ይችላል ብሎ መገመት የዓለምን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚገባ ጠጋ ብሎ ለመመርመር አለመቻልና በነጻ ገበያ ርዕዮተ-ዓለም ላይ ብቻ ዕምነት መጣል ነው። በተጨማሪም ኒዎ-ሊበራሊዝም ማለት ምን ማለት እንደሆነና የሚያመጣውንም ጠንቅ በሚገባ ለመገንዘብ አለመፈለግ ነው።
ኢትዮጵያ አባል የመሆን ዕድል ብታገኝ፣ 20 ዐመት ያህል በኒዎ-ሊበራል ስም ካካሄደችው የነጻ ገበያ ከደረሰባት ጉዳት በተጨማሪ በቀላሉ መጭው ትውልድ ሊቀርፈው የማይችል አደጋ ውስጥ ትወድቃለች። በመጀመሪያ ደረጃ ገበያዋን ልቅ ማድረግ ስላለባት ወደ ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ተመሳሳይ ምርቶችን ያዳክማሉ። ለምሳሌ ቻይና በአሁኑ ጊዜ ምርቷን በርካሽ ዋጋ በማምረትና በዓለም ገበያ ላይ በማራገፍ የደካማ አገሮችን የምርት እንቅስቃሴዎችን ማዳከም ብቻ ሳይሆን፣ የኢንዱስትሪ አገሮችንንም እየተጋፋችና ገበያቸውን እያጣበበች ነው። ብዙ ኢንዱስትሪ አገሮች ውበትና ጥራት የሌላቸው የቻይና ጫማና የጨርቃ ጨርቅ ምርት ውጤቶች ማራገፊያ በመሆን አንዳንድ አካባቢዎች ወደ ሶስተኛው ዓለም አገሮች ሁኔታ እየተለወጡ ነው። በዚህ መልክ ኢንዱስትሪዎችም በዝቅተኛ ዋጋ እናመርታለን በማለት ኢንዱስትሪያቸውን ቻይናና ሌሎች ርካሽ የሰው ጉልበት ያለበት አገር ወስደው በመትከል ብዙ ሰራተኞችን ከስራ መሰካቸው እንዲባረሩ ሆነዋል። ወደ ኢንዱስትሪ አገሮች ስንመጣ ደግሞ በተለይ በድጎማ የሚመረተው የእርሻ ምርት ውጤት በዓለም ገበያ ላይ እየተራገፈ ብዙ የሶስተኛው ዓለም ገበሬዎችን እየመታና ወደ ድህነት እየገፈተረ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነት የተስፋፋውና መንግስታትን እሰካማባረር የተደረሰበት አንደኛውና ዋናው ምክንያት ይህ ዐይነቱ የነጻ ንግድ ልቅ በሆነ መልክ መስፋፋቱ ነው። ከዚህ ስንነሳ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሳትሆን በከፍተኛ ደረጃ የምትጎዳና ከአሁኑ የባሰ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል እንደሚደርስባት ከአሁኑ መተንበይ ይቻላል።
ወደ ባንኩና የቴሌኮሙኒኬሽን መስክ እንምጣ። ኤህአዴግ ስልጣን ከያዘና የነፃ ገበያ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ብዙ የግል ባንኮች ተቋቁመዋል። ይህ ግልጽ እየሆነ ለምን የንግድ ድርጀቱ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትን ባንኮች ወደ ግል ማዛወር አለባችሁ እያለ እንደሚወተውት ሊገባኝ አይችልም። እንደሚታወቀው በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በግል ከሚንቀሳቀሱ ባንኮች ውጭ በመንግስትም ቁጥጥር ስር ያሉ በክፍለ-ሀገርና በስቴት ደረጃ የተደራጁ ባንኮች አሉ። ለምሳሌ የጀርመንን የባንክ አወቃቀር ብንወስድ ሶስት ዐይነት የባንኮች አወቃቀር አለ። ከማዕከላዊ ባንኩ በስተቀር፣ በዋናው መንግስትና በየፌዴራል ስቴቶች ቁጥጥር ስር ያሉ ለማዕከለኛና ለትናንሽ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ለቤት ሰሪዎች በርካሽ ብድር የሚሰጡ አሉ። ሁለተኛ፣ በህብረት ስር የሚተዳደሩና ለአባሎቻቸው ብድር የሚሰጡ። የማህበራዊ ነክ ድርጅቶች ከመንግስት የሚያገኙትን ድጎማ በነዚህ ባንኮች አማካይነት ነው የሚተላለፍላቸው። ሶስተኛ፣ በግል ስር ያሉ ባንኮች። ከዚህ ውጭ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ የኢንቬስትሜንት ባንክ አለ። ይህ ዐይነቱ አጠቃላይ የባንክ ስይስተም አወቃቀር ዩኒቨርሳል ባንክ ይባላል። ባለፉት ስድሳ ዐመታት የጀርመን የባንክ አወቃቀርና አሰራር በዚህ መልክ ሲካሄድ የቆየ ነው። በ2007 ዓ.ም ከተከሰተው ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ቀውስ ወዲሀ ብዙ የግል ባንኮች ከመንግስት ድጎማ እያገኙና አንዳንዶችም በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ተደርገዋል። ብዙ ተቋሞችም፣ ለምሳሌ እንደ ባቡር ያሉ፣ የከተማ ውስጥ የውስጥ ለውስጥ መገናኛዎች፣ የጤና መሰኮችና ትምህርት ቤቶች በብዙ ኢንዱስትሪ አገሮች በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። ለምሳሌ የፈረንሳይ መንግስት ባለፉት ስድሳ ዐመታት ዕውቅ የሆነ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ የሚያካሂድና ብዙ ተቋሞችንም በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ዕድገታቻውን ያመቻቻል። እነዚህን አገሮች የግዴታ በመንግስት ስር ያሉ ተቋሞችን ወደግል አዘዋውሩ እያለ የሚጨቀጭቃቸው የለም። ሀቁ ይህ ከሆነ ለምንድነው የንግድ ድርጅቱ የአቶ መለሰን መንግስት የሚጨቀጭቀው? የገንዘብን ዕድገት ትርጉምንና እንዲሁም ባንክ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ስላለው ሚና በሚመለከት እ.ኢ.አ በ1991 በሚያዚያ ወር በጦብያ መጽሄት ላይ አንድ ጽሁፍ ስላወጣሁ እሱን መመልከቱ አንዳንድ ነገሮችን ግልጽ ሊያደርግ የሚችል ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ የመንግስት ባንኮች ወደ ግል ቢዘዋወሩ ብድር ፈላጊዎች የሚፈልጉትን ብድር በተመጣጣኝ ወለድ ሊያገኙ አይችሉም። በተለይም የባዝል የባንክ ስምምነት የሟሟላት ጉዳይ ብዙ ባናኮችን ችግር ውስጥ ሊከታቸው ይችላል። ከብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ልምድ የምንቀምሰው እንዲያውም በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች መሀከል ያለው ግኑኝነት ከመላላቱ ባሻገር የገንዘብ መሽከርክር ኃይል ይቀንሳል። አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጠርና ሊከማች አይችልም።
የስልክንም ጉዳይ ስንመለከት የተሻለ ዕድል ማየት አንችልም። አንዳንድ ቦታዎች ለማመልከት እንደሞከርኩት ባለፉት አስራዘጠኝ ዐመታት በተንቀሳቃሽ ስልክ መስፋፋት የተነሳ ቋሚው ስልክ እየተዳከመ መጥቷል። ወደ ግልሀብትነት ቢሸጋገር የቀረው ቋሚ ስልክ የባሰውን ይዳከማል። ምክንያቱም ኢንቬስተሮች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ለመሽጥና ትርፍ ለማካበት ሲሉ ወደ ቋሚው ስልክ ላይ ብቻ ስለማያተኩሩ ነው። የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ልምድ ይህንን ነው የሚያስተምረን። ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በ90ዎቹ ዐመታት ውሀን፣ ስልክን፣ መብራትንና ሌሎችንም የመንግስትን ተቋማት ለዓለም አቀፍ ኩባንዎች ከሸጡ በኋላ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያየለ በመምጣቱና ኩባንያዎችም አዳዲስ መዋዕለ-ነዋይ ከማካሄድ ይልቅ ትርፉ ላይ ማትኮር ብቻ ስለሆነ ተግባራቸው መንግስታት ተቋሞቸን መልሰው እንዲገዙ ተገደዋል። በኢንዱስትሪ አገሮችም በተለይ እንደ ውሀና መብራት የመሳሰሉት እንደገና በመንግስት ቁጥጥር ስር እየሆኑ ነው ወይም እየገዟቸው ነው። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለና አሁን ደግሞ በተለይም የአገራችን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየተዳከመ በመጣበት ጊዜና የህዝቡም የመግዛት አቅም አጅግ በተዳከመበት ወቅት ለምን አባል ለመሆን ጥድፊያ እንደተያዘ በፍጹም አይገባኝም። ለምንስ የባንኩም ሆነ የተሌኮሙኒኬሽን መስኩ መሸጥ አለበት እየተባለ ይወተወታል ?
ያም ሆነ ይሀ ከንግድም ሆነ ከአጠቃላይ ኢንቬስትሜንት አንጻር ስንነሳና ሁኔታውን ስንገመግም የእነ አቶ መለስና የንግድና ኢንዱስትሪ ምኒሰተሩ አካሄድ በምንም ዐይነት ወደ ውስጥ፣ የውስጥ ገበያን በተስተካከለ መልክ ሊያሳድግና አብዛኛውን ህዝብ ሊያሳትፍ የሚችል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር የሚያግዝ አይሆንም። የኤህአዴግ አገዛዝ ከዚህ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ የሙጥኝ እስካለ ድረስና ፍልስፍናው በነጹህ የገበያ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ የግዴታ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚው ውስጥ ከመግባት ሌላ ዕድል የላትም የሚለው እንደመመሪያ እስከተወሰደ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች በዚህም ሆነ በሌላ አገዛዝ የስልጣኔን ብርሃን ሊጎናጸፉ በፍጹም አይችሉም። አገራችን በሚቀጥሉት ሃምሳና መቶ ዐመታት አዲስ ብቅ እያለ በሚመጣና ንቃተ-ህሊናው ዝቅተኛ በሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት እያታሸች ለዘለዓለም ታልፋ የምትቀር አገር ትሆናለች ማለት ነው።
ፈቃዱ በቀለ
fekadubekele@gmx.de