[gtranslate]

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ነው ወይስ  የኋሊት ጉዞ እያሳየ ነው ?  የህዝቡስ ኑሮ

ተሻሽሏል ወይ ? ወይስ ጥቂቶች የደለቡበት ሁኔታ ነው የሚታየው ?

 ዶ/ር ዳንኤል ተፈራና ዶ/ር ፀሀይ ለኢሳት ጋዜጠኛ ለአቶ ፋሲል የኔ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለቀረቡላቸው

                   ጥያቄዎች ለሰጧቸው መልሶች የቀረበ አስተያየት- ከፈቃዱ በቀለ !

 

መግቢያ

በቅርቡ ሁለት በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶችን የኢሳት የቴሊቪዝን ጋዜጠኛ የሆነው አቶ ፋሲል የኔ ዓለም ኢትዮጵያ ከውጭ የምትበደረው ብድር መጠን እያደገ ስለመምጣቱና ስለኢኮኖሚው አጠቃላይ ሁኔታ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በመጋበዝ በመሰላቸውና በሚታያቸው፣ እንዲሁም ከተማሩት የኢኮኖሚ ትምህርት አንፃርና ከዕምነታቸው በመነሳት ለተደረገላቸው ጥያቄ አስተያየት ለመስጠት ሞክረዋል። ፕሮፊሰር ዳንኤል ዕዳንንም ሆነ፣ የሚሰሩትን ፕሮጅክቶች ወደ ፊት ሊገኝ ከሚችለው ውጤትና አትኩሮ ቅድሚያ መስጠት የሚገባውን፣ ነገር ግን የሚታለፈው አንገብጋቤ ጥያቄ ሊያስከትል የሚችለውን  አሉታዊ ውጤት በንጽጽር መልክ ለማሳየት ሲሞክር፣ ዶ/ር ፀሀይ ደግሞ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ቢሰሩ ጥቅማቸው እንደሚያመዝንና ለዕድገትም አስፈላጊ መሆናቸውን ለማመልከት ሞክሯል።

በመሰረቱ በሁለቱ ኢኮኖሚስቶቸ መሀከል ያለው ልዩነት በዚህ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በመንግስት ሚናና መንግስት አትኩሮ ስለሚሰጠው ጉዳይ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ስላሉ „የልማት አውታሮች“  በሚባሉት እንደ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሙኒኬሽንና የአውራ ጎዳና ባለስልጣን ጉዳይና፣ ሰለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ስለነዚህ „ትርፋማነትና“፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ  በኩል፣ እነዚህ ድርጅቶች የሚበደሩት ብድር በመንግስት ብድር ውስጥ ተጠቃሎ መታየት ስላለበት ጉዳይና፣ እንዲሁም ወደ ግል ስለመዘዋወራቸው፣ ወይም አለመዘዋወራቸው፣ በመንግስት ላይ ስለሚያደርጉት ጫና፣ ሁለቱም ኢኮኖሚስቶች የተለያየ ግምትና አስተያየት ሰጥተዋል። እንዲሁም መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ሰለሚጫወተው ሚና፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ስለመሬት ይዞታና ወደ ግል ሀብትነት ስለመዘዋወር ጉዳይ የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ከቃለ-ምልልሱ መረዳት ይቻላል።

በሁለቱ ኢኮኖሚስቶች ስለተሰጠው የቃለ-ምልልስና ገለጻ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቢያስመስልም፣ የሁለቱም ምሁሮች የኢኮኖሚ ትንታኔ የቲዎሪ መነሻ አንድ ነው ። ይኸውም የኒዎ-ሊበራል ወይም የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊስ ላይ  ይስማማሉ። ሁለቱም አቀራራባቸው የተለየ ቢመስልም፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግር በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አማካይነትና በውጭ መዋዕለ-ነዋይ(Foreign Direct Investment) እንደሚፈታ ያላቸውን አቋም፣ ከዚህ አስተያየታቸውም ሆነ  አልፈው አልፈው ለሚዲያ ከሚያቀርቡት ጽሁፎቻቸው መገንዘብ ይቻላል።  የመንግስት ጣልቃ ገብነት ዛሬውኑ መቆም አለበት፣ ሁሉም ነገር በነፃ ገበያ አማካይነት ሊወሰን ይችላል በሚለው ላይ በመሀከላቸው ያለው የጊዜ እንጂ ፣ በመሰረቱ የአቋም ልዩነት እንደሌላቸው መገንዘብ ይቻላል።

በሌላ በኩል የሁለቱን ኢኮኖሚስቶች አስተያየት ለተመለከተ ተፍታቶና ተብራርቶ ቀለል ባለ መልክ የቀረበ አይደለም። ከመስራት፣ ገንዘብ ከማግኘትና በገንዘቡ ገበያ ላይ ወጥቶ የሚፈልገውን ነገር ለመግዛትና በመጠቀም ለሚኖር ሰውና፣ የኢኮኖሚን ትርጉም በሚገባ ለማይረዳ የሁለቱ ኢኮኖሚስቶች አቀራረብ ቀለል ብሎ ማንኛውም ሰው ሊረዳው በሚችለው መልክ የቀረበ አይደለም።  አቀራረባቸውም ከንጹሁ የኒዎ-ሊበራልና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመነሳት የቀረበ አስተያየት ስለሆነ የኢኮኖሚን ፅንሰ-ሃሳብ ትርጉሙንና በተግባር በሚመነዘርበት ጊዜ ሊያስከትል የሚቸለውን አዎንታዊና አሉታዊ ውጤት ለመረዳት ለሚፈልግ በቀላሉ ትምህርት ሊቀስም በፍጹም አይችልም። በተጨማሪም፣ ሁለቱም ኢኮኖሚስቶች የኢኮኖሚን ጥያቄ ከሌላው የህብረተሰብ ጥያቄ፣ የፖለቲካ፣ የማህበረሰብና የህብረተሰብ ግንባታ፣ እንዲሁም የህብረ-ብሄር ግንባታና የባህል ሁኔታ ነጥለው በማየታቸውና፣ ኢኮኖሚን በአየር ላይ የሚንቀሳቀስና የሰውም ልጅ ፍላጎት ገንዘብ ከማግኘት ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም የሚል አቀራረብ ስለሰነዘሩና፣ እንደዚህ ዐይነቱ አመለካከት ቶሎ ብሎ ካልታረመ ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊመራን ስለሚችል ነገሩን ጠለቅ ብዬ እንድመረምር ተገደድኩኝ። ከዚህም በላይ፣ ሁለቱም ኢኮኖሚስቶች በንጹህ መልኩ በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክ ቲዎሪ የሰለጠኑ ስለሆነ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ትርጉምና ስለ ህብረተሰብአዊ የሀብት ክምችት ፈጠራና ሁለ-ገብ ለሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትና የህብረተሰብ ግንባታ ሊናገሩ በፍጹም አይችሉም።  በመሆኑም በኢኮኖሚ ዕድገት ክንዋኔ ውስጥ የተቀላጠፈና የሰለጠነ ኢንስቲቱሽን ከታች ወደ ላይ እንዴት መዋቀር እንዳለበት፣ መንግስት ስለሚባለው ነገርና ምንነት፣ እንዲሁም በየጊዜው ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር እየታየ ጥገናዊ ለውጥ ስለማስፈለጉ ጉዳይና፣ ጥገናዊ ለውጥ ወይም መሻሻልን የማያሳይ መንግስታዊ መዋቅር ለኢኮኖሚና ለአጠቃላዩ የህብረተሰብ ዕድገት የቱን ያህል መደናቅፍ ሊሆን እንደሚችል ሊያመልክቱና ሊያብራሩ አልቻሉም። ከአገላለጻቸው መረዳት እንደሚቻለው፣ መንግስት የሚባለው ነገር እንደተሰጠና ወይም ደግሞ በአንዳች ኃይል ከላይ ወደ ታች እንደተቀመጠ፣ መለወጥም እንደሌለበት ቅዱሳዊ ኃይል አድርገው ነው የተረዱት  የሚያስመስላቸው። በሌላ አነጋገር፣ መንግስትና አገዛዝ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ያህል፣ በሌላ ወገን ግን መንግስታዊ አወቃቀር በአንድ አገዛዝ ለሱ በሚበጅ መልክ በመዋቀርና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር ወደ ጨቋኝ መሳሪያነትና ወደ ተራ ዘራፊ መንግስትነት(Predatory State) እንደሚለወጥ ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም። ስለሆነም ሰለ መንግስት እየደጋገሙ ቢያወሩም በአገራችን ምድር ውስጥ ምን ዐይነት መንግስት እንዳለ ሊያብራሩ በፍጹም አልቻሉም።

ከዚህ ስነሳ በአገራችን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከፈጠራና ከህብረ-ብሄር ግንባታ ጋር ያልተያያዘውን ሩጫ ስመለከት የኢኮኖሚ ፅንሰ-ሃሳብ የቱን ያህል በተሳሳተ መልክ እንደተተረጎመና እንደሚተረጎም፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ እንደሚያሳስተውና መንፈሱን እንደሚመረዘውና እንደመርዘው መገመቱ ከባድ አይሆንም። በመሆኑም ሁለቱ ኢኮኖሚስቶች የሰጡት አሰተያየት ብዙ ግራ የሚያጋቡና ከኢኮኖሚ ሳይንስ አንጻር የማይጣጣሙ አቀራረቦች ስለሆኑ አነዚህን በቅደም ተከተል ለማብራራት ተገደድኩኝ። በመጀመሪያ ኢኮኖሚስቶች በሚለው አባባል ላይ ማብራሪያ ለመስጠት እፈልጋለሁ።

አንድ ዐይነት የኢኮኖሚ አስተሳሰብ፣ ወይስ የተለያየ አስተሳሰብና

የተለያየ አመለካከት ያላቻው ኢኮኖሚስቶች !

በአገራችን የተለመደና፣ በሰፊው የሚወራና የሚፈራ እንዲሁም የሚከበር አነጋገር አለ፤ ይኸውም ኢኮኖሚስቶች የሚለው አባባል ነው። ኢኮኖሚም የቁጠባ ትምህርት እየተባለ ነው የሚታወቀው። ኢኮኖሚክስ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት የሚነደፍበት፣ የአንድን አገር የማቴሪያልና የሰው ሀብት በማንቀሳቀስ፣ እንዲሁም አዳዲስ መሳሪያዎችን በመፍጠር ወደ ተሻለና ህዝብን ርስ በርስ ወደሚያስተሳስር ስርዓት ለመሸጋገር የሚያስችል ታሪክ መስሪያ ዕውቀት ሆኖ አይደለም እንድንገነዘብ የተደረገው።  እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመና፣ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መሰጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኢኮኖሚ ሙያ የሚሰለጥኑት በሙሉ አንድ ዐይነት አመለካከት ይዘው ስለሚመረቁ፣ ይህ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት የሚነደፍበትና አንድ ህዝብ ታሪክ እንዲሰራ የሚደረግበት የዕውቀት ዘርፍ የባሰውን ወደ ድህነት የሚገፈትርና ብሄራዊ ነፃነትን የሚያስገረስስ ሊሆን በቅቷል። በተጨባጭም የታየውና የሚታየው ይህ ነው። ሁሉም ተማሪዎች በኒዎ-ክላሲካልና በኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ የሚሰለጥኑ ስለሆነ በስራ ዓለም ውስጥ በሚሰማሩበት ጊዜ ስራቸው በምድር ላይ ከሚታየውና ከተጨባጩ የህዝባችን ኑሮ ጋር የማይጣጣም ይሆናል። የአገራችንንም የኢኮኖሚ ሁኔታ ከተማሩበት እጅግ አበስትራክት ከሆነ ቲዎሪ አንጻር ‘ስለሚገመግሙ’ የህብረተሰባችንን ውስጣዊ ህግ፣ የዕድገት ማነቆና በየጊዜው ተግባራዊ የሚሆኑትን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አዎንታዊና ወይም አሉታዊ ውጤታቸውን  በዲያሌክቲክ መነጽር  ለመመርመር የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ ላይ የተመሰረተው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ፣ ስልጣኔና ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ ለምን የተቃራኒውን ያስከትላል? ብለው ለመመርመርና የፓራዳይም ለውጥ(Paradigm  Change)  ለማምጣት በፍጹ አይችሉም፤ ወይም አቃጡም። አንድ ወጥ ከሆነውና በጭፍኑ ተቀባይነትን ያገኘውን  የኢኮኖሚ ፖሊሲ እየደጋገሙ ተግባራዊም ስለሚያደርጉ የህብረተሰባችን ችግር ጥልቅና ውስብስብ እየሆነ እንዲመጣ ከማድረግ በስተቀር በመጨነቅ  የህዝባችንን ችግር ሊፈታ የሚችል፣ በተለያዩ አገሮች በተግባር የተተረጎሙና ፍቱን መፍትሄ ሊያመጡ የቻሉ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥሩ አይታይም። „ወደድንም ጠላንም ሁሉም አገር ተመሳሳይ የማክሮ አኮኖሚክ ፖሊሲ ያስፈልገዋል“ በማለትና በማስፋፋት የህዝባችንን የስልጣኔ ጥም ሲያራዝሙና፣ ኢትዮጵያችንም በዘለዓለማዊ ለማኝነት እንድትታወቅ ሳያውቁት ዋናው የዕድገት ማነቆና ለተወሳሰበ ድህነት ምክንያት በመሆን ህዝባችን ኑሮው ጨልሞበት በዘለዓለም ድንቁርና ውስጥ እንዲኖር  ያደርጋሉ።

ይህ ዐይነቱ የተዛባና ጭፍን አመለካከት በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በብዙ የአፍሪካና በአሲያ አገሮችም በመስፈን በእነዚህ አገሮችም ውስጥ ስሙን እየለዋወጡ በይዘት ግን ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በታወቁ ኤክስፐርቶች እየወጡ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ ህዝቦች ከብልጽግናና ከተደላደለ ኑሮ ይልቅ ወደ ድህነትና ወደ መሰደድ እንዲያመሩ ተገደዋል፤ እየተገደዱም ነው። ስለዚህም በአለፉት ስድሳ ዐመታት በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተካሄዱት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ በዕውቅ የወጡና ሰፊውን ህዝብ ለማድኸየትና ጥቂቱን አበልጽጎ በዓለም የስልጣን ሂራርኪ ውስጥ በማካተት አንድ አገር የስልጣኔ ባለቤት በመሆን የተከበረችና የኮራች አገር እንዳትገነባ  የተወጠነ ሴራ ለመሆኑ ለብዙዎቻችን ግልጽ አይደለም። ይህንን ሴራና የሰውን አስተሳሰብ ጭፍን የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያጋልጠውን በብዙ ሺህ ገፆችና መጽሀፎች ተጽፎ የቀረበውን እንደሌለ በማለፍና በማጥላላት ወይም የኮንስፒራሲ ቲዎሪ ነው በማለት  አንድ ህዝብና ታዳጊ ወጣት ዕውነቱን ከውሸት እንዳይለይና ታሪክን እንዳይሰራ በግልጽ ታግዷል።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት ሲደረግ መሰረታዊ ዓላማው በሁሉም አገሮች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና፣ አነሰም በዛም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕኩልነትን ለማስፈን ሳይሆን፣ በየአገሩ አዳዲስ ተቀጣይ መንግስታትና(Vassal Sates) አቀብቃቢዎች በመፍጠርና በማስተማር አንድ ህዝብ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖርና፣ በዚያውም ሀብቱ እንዲዘረፍ ለማድረግ ነው። በመሆኑም፣ አብዛኛዎቹ የላቲንና የአፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ የሚደገፈውን የአሜሪካንን እሴትና ጥቅም የሚያንፀባርቀውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመገደድ ስድሳ ዐመታት ያህል ዕዳ ከፋይና ተበዝባዥ በመሆን ፍዳቸውን እንዲያዩ ተደርገዋል ። ባልተስተካከለ ንግድም(Unequal Exchange) በረቀቀ መልክ የካፒታሊስት አገሮችን የሀብት ክምችት ዕድገት ሊያፋጥኑ ችለዋል። ይህ ሁሉ ምዝበራ የተካሄደውና የሚካሄደው በነፃ የገበያ አኮኖሚ ፖሊሲ መርሆች ስም ሁለም ነገር እንዲደነገግና የህዝቡም አስተያየት በንጹህ የንግድ ልውውጥ ዙሪያ እንዲሽከረከር በማድረግ ነው። የሁለቱም ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖች እየተባሉ የሚጠሩት ዋና ተግባርም በረቀቀ ዘዴ የአፍሪቃና የላቲን አሜሪካ አገሮች የጥሬ ሀብት የሚዘረፍበትን መንገድ ማማቻቸት ነው። ለዚህ ዐይነቱ የረቀቀ ዘረፋ የአንጀት አጥብቅ ፖሊሲና(Austerity Program) ብድር ዋና መሳሪያዎች በመሆን ሀብት ከነዚህ ደካማ አገሮች ወደ ካፒታሊስት አገሮች በመፍሰስ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የካፒታሊዝምን የሀብት ክምችት አፋጥነዋል። በዚህም መልክ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ የተዛባ ሁኔታ በመፍጠር በደሀና በሀብታም መሀከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ ለማድረግ በቅተዋል።  አሁን በቅርቡ በቶማስ ፒኬሊ የወጣው ካፒታሊዝም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን በመባል የሚታወቀው መጽሀፍ የሚያብራራውና፣ በራሳቸው በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ተቀባይነትን ያገኘው ኢምፔሪካል ጥናት የሚያመለክተው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በካፒታሊዝም አማካይነት በጥቂቶች እጅ ብዙ ሀብት  እየተከማቸና በተለያየ መልከ የሚገለጽ ድህነት እንደተስፋፋ ነው። ከዚህ ትንተናና ከብዙ ትችታዊ ኢምፔሪካል ጥናቶች ስንነሳና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙከራ የተደረገባቸውን አገሮችና በምድር ላይ የሚታየውን ሁኔታ ስናይ፣ ስለ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፍቱነትና ዕድገትን አምጭነት በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚክስ ምሁራን የሚቀርበው ሀተታ እጅግ አደናጋሪና አንዳንዴም ሆን ብሎ የሚቀርብ ነው የሚመስለው።

በተለይም በዶ/ር ዳንኤል ተፈራ የነፃ ገበያን ጠቃሚነት፣ ዕድገትንና ዕኩልነትን አምጭነት አስመልክቶ አልፎ አልፎ በድህረ-ገጽ ላይ የሚያቀርባቸውን ጽሁፎች በትዝብታ እንድንመለከተው ተገደናል። ለነፃ ገበያ ያለውን ዕምነትና ጥብቅናም በኢሳት የቴሌቪዠን ጣቢያ ላይ ተጋብዞ በተጠየቀበት ጊዜ እንደገና አረጋግጦልናል። የነፃ ገበያን ፖሊሲን ተግባራዊነት በሚመለከት በተለያዩ ጽሁፎቹ ውስጥ፣ እሱ እንደሚለው ተግባራዊ የሆነና እኩልነትንም ያመጣ ሳይሆን፣  በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ሆን ተብሎ የሚሰበክ እንጂ በታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የካፒታሊስት አገሮች ዛሬ ነፃ ገበያ እየተባለ የሚወደሰውንና ሁሉም አገሮች እንዲመኙትና እንዲያልሙት የተደረገውን ከማየታቸው በፊት ብዙ ውጣና ውረድን አልፈዋል። የተለያዩ የአውሮፓ አገሮችን የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ታሪክ ብንወስድና ብንመረምር እንኳ፣ ከእንግሊዝ በፊት የተወሰነው የኢጣሊያን ክፍል በአስራአምስተኛውና በአስራስድስተኛው ክፍለ-ዘመን በዕድገት ቀድሞ የሄደ ነበር። እንግሊዝ ከጣሊያን ከቀዳችና፣ ከሆላንድ ፈልሰው የመጡ ነጋዴዎችና አንጥረኞችን፣ እንዲሁም ምሁራንን ካገኝችና ካሰማራች በኋላ ሆን ብላ የተከተለችው መንገድ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ነበር። ይህ ዐይነቱ ወደ ውስጥ ያተኮረ፣ በማኑፋክቱር ላይ የተደገፈና፣ የጥሬ-ሀብትን ሳይፈበረክና እስከመጨረሻው ድረስ ሳይመረት እንዳይወጣ በጊዜው እንግሊዝን ይገዛ የነበረው ሃይንሪሽ ስምንተኛው የሚባለው ንጉስ ተግባራዊ ያደረገውና የመንግስቱም ዕውቅ ፖሊሲ ነበር። ይሁንና ግን በጊዜው አዲሱን የኢኮኖሚ ግንባታ በሚያራምዱና የሳይንስንና የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት በሚሰብኩ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ዕምነት ተከታዮችና፣ አዲሱን ሳይንስና የኢኮኖሚ ዕድገት በሚቀናቀኑ  የካቶሊክ ሃይማኖት ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የጦፈ ጦርነትና ትግል፣ እንዲሁም መገዳደል ይካሄድ ነበር። ቀስ በቀስ ካፒታሊዝም እየተስፋፋና ሳይንስም ተቀባይነትን እያገኘ ሲመጣ የካፒታሊዝም ወደ ገጠሩ ውስጥ መስፋፋት ገበሬውን ከመሬቱ እያፈናቀለው ነው የመጣው። ከመሬቱ የተፈናቀለውም ገበሬ ወደ ለንደንና ወደ ሌሎች የማኑፋክቱር ተከላ መስፋፋት በጀመረባቸው የእንግሊዝ ከተማዎች ሲሰደድ ወዲያውኑ የስራ መስክ የማግኝት ዕድል አልነበረውም።  ብዙ የታሪክ ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት የእነ አዳም ስሚዙ የነጻ ገበያ ፍልስፍና ከመጻፉ በፊት እንግሊዝ ኢኮኖሚዋን በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መርሆች አማካይነት ሳይሆን የገነባችው፣ ከውስጥ በበግ እርባታ ላይ የተሰማራውንና የበግ ጸጉር በመሸጥና ገንዘብ ማካባት የጀመረው የከበርቴ መደብ ገበሬውን በማፈናቀልና ወደ ድህነት በመግፈተር ሲሆን፣(Primitive Capitalist Accumulation) በሌላ ወገን ደግሞ መንግስት ጥብቅ የመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማካሄድ ነበር። ይህም ማለት፣ የውስጡ ገበያና እንግሊዝ አገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከውጭ በሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች እንዳይጎዱ የታሪፍ ዕገዳ ፖሊሲ በማካሄድ ሲሆን፣ በተጨማሪም መንግስት በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ በመሰማራትና ሁኔታውን በማመቻቸት ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነበር። በሌላ አነጋገር፣ የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ እንደ መጽሀፍ ቅዱስ እስከታወጀበትና መሰበክ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ የእንግሊዙንም ሆነ የሌሎችን የምዕራብ አውሮፓን የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ታሪክ ለመረመረ የሚገነዘበው በቅራኔዎች የተሞላና ቀስ በቀስም ግልጽ ሆኖ በወጣ ህብረተሰብአዊ የጥቅም ትግል የሚገለጽ ነበር። በኢንዱስትሪ አብዮት መስፋፋትና በካፒታሊዝም ዕድገት የተነሳ አሰልቺና ተደጋጋሚ እንዲሁም በዝባዠ ስርዓት በመፈጠሩ ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎች አያየሉ ሊመጡ እንደቻሉም በሚገባ ተመዝግቧል። ይህንን የተመለከቱ ምሁራን ሁኔታው አይ እንዲሻሳል፣ ወይም በአዲስና ዕኩልነትን በሚያሰፍን ስርዓት እንዲተካ ከፍተኛ ትግል ማድረግ እንደጀመሩ የታወቀም ጉዳይ ነው።ይሁንና ግን ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ እንደመጣ እንደዚሁ ታሪክ ያረጋግጣል።

ለመጀመሪያ ጊዘ በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ላይ የኃይል ሚዛን እያሸነፈ ሲመጣ ሙሉ በሙሉ የነፃ ገበያ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲደረግ በእንግሊዝ አገር ሰፊው ህዝብ የባሰ ደሃ እየሆነ ይመጣል። ከሰላሳ ዐመት ሙከራ በኋላ የድሆች ህግ (Poor Law) በመባል የሚታወቀውን በማውጣት ሁሉም ሰው በጣም በዝቅተኛ ደሞዝ ተቀጥሮ  ማንኛውንም ስራ እንዲሰራ ይገደዳል። ይሁንና ግን እንግሊዝ ሙሉ በሙሉ የነጻ ገበያ ሞዴል ወደ ውስጥ ተግባራዊ ከማድረግ ብትቆጠብም ወደ ውጭ ግን መስበከ የጀመረችው ዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍልና የነፃ ገበያ የሚሉትን መርሆች ናቸው። እያደገና እየተስፋፋ የመጣው የኢንዱስትሪ ተከላ የግዴታ የጥሬ-ሀብት ስለሚያስፈልገው በነፃ ንግድ አማካይነት ጥሬ-ሀብትን የምትቆጣጠርበትንና የምትዘርፍበትን መንገድ ማመቻት ተያያዘች። የነፃ ንግድ የሚያመጣውን አደጋ የተረዱና በነፃ ንግድም አማካይነት መጥፎ ልምድን ያካበቱ እንደ ጀርመን፣ በኋላ ደግሞ አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮች የመርካንታሊስት ወይም በመንግስት የተደገፈ ፖሊሲ በመከተል ኢኮኖሚያቸውን መገንባት ጀመሩ። እነዚህ በመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተደግፈው ኢኮኖሚያቸውን መገንባት የጀመሩ አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንግሊዝን እየተወዳደሩ በመምጣት የዓለም ገበያን ወደ መቆጣጠር አመሩ። ይሁንና ግን በሁሉም አገሮች የተዋቀሩት አገዛዞችና የመንግስት አውታሮች የጠቅላላውን ህዝብ ዕድገት የሚያግዙና የሚወክሉ ሳይሆኑ በመንግስት ፖሊሲ ላይ ጫና ለሚያደርጉ ኃይሎች የሚያመቹና በሀብት እንዲካብቱ ያደረጉ በመሆናቸው በሁሉም አገሮች በአፍላው ወቅት ድህነት የተስፋፋበትና የሰራተኛውም ኑሮ አሰቃቂ እንደነበር ኢምፔሪካል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። መሬትም በጥቂት ከበርቴዎች ቁጥጥር ስር በመውደቅና፣ እንዲሸጥና እንዲለወጥ በመደረጉም፣ አብዛኛው አራሽ ገበሬም መሬትን ተከራይቶ የሚያርስ እንጂ የመሬት ባለቤትነት ዕድል አላገኘም። የመሬት መሸጥና መለወጥ ወይም መከራየት የእርሻ ምርትን ዋጋ ከፍ እንዲል በማድረጉ መሬትን እየተከራየ የሚያርሰው ገበሬ በካፒታሊዝም መስፋፋት የተነሳ በብዙ መንገዶች እንዲበዘበዝና ጥገኛም እንዲሆን ሊደረግ በቅቷል።  ከዚህ ስንነሳ የገበያ ኢኮኖሚ ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ እንደሚለን በነፃ መንገድ ያደገና ሁሉንም በዕኩልነት እንዲበለጽጉ ያደረገ ሳይሆን፣ አስከፊና በዝባዠ ስርዓት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን።

ሀቁ ይሆ ሆኖ ሳለ በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ተጨባጩንና በተግባርም የታየውን ነገር እንዳልነበረ በማድረግና በመጻፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃ ገበያን ፍልስፍና በማስፋፋት ብዙ አገሮችን ማሳሳት ተችሏል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ከ1880 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ በኩል ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን የማርክስን ዳስ ካፒታል ለመታገል ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከፊዚክስ እንዳለ የማቲማቲክስ ሞዴሎችን በመቅዳት በነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት በህብረተሰብ ውስጥ በሁሉም መስክ ሚዛናዊ  ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚለውን የተፈጥሮን ህግ አካሄድ ከህብረተሰብ ዕድገት ጋር መካኒካል በሆነ መልክ ለማጣጣም በመሞከር የኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚ ቲዎሪ በመዳበሩና በመስፋፋቱ ነው። ይህ ዐይነቱ ዕምነት በመስፋፋቱና መንግስታትም እንዲያምኑ በመደረጋቸው በየጊዜው በመንግስት  የሚደገፉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ በማድረግ በተለይም በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ከፍተኛና ተከታታይ የእኮኖሚ ቀውስ ሊከሰት ችሏል። ብዙ የኢኮኖሚክ የታሪክ አዋቂዎችም ሆነ ኢኮኖሚስቶች፣ ኬይንስም ጨምሮ በተለይም ለጀርመኑ የፋሺዝም ዋናው መነሻ፣ በአንድ በኩል ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በጀርመን ላይ በቨርሳይሉ ስምምነት የተደረገባት የካሳ ክፍያ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በጊዜው የነበረው አገዛዝ የወዝ አደሩ መሪዎች ያቀረቡትንና ለብዙ ሚሊዮን ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት የሚችለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለመቀበሉና፣ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተሉ ነው። ይህ ፖሊሲና የጀርመኑ የካሳ ክፍያ በጀርመን ምድር ለአምስት ሚሊዮን የስራ አጥነትና ለድህነት ምክንያት ሲሆን፣ ለፋሺዝም ልዩ የሆነ አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ጀርመን ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት በተለይም ፖላንድን፣ ቼኮዝላቫካይንና ሶቭየት ህብረትን በመውረርና በአውሮፕላን በመደብደብ ወደ ሃምሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንዲያልቅና ኢኮኖሚያቸው እንዲከሰከስና ከተማዎች እንዲፈራርሱ ለማድረግ በቅታለች። በሌላ አነጋገር የታሪክ ግዴታ ይሁን አይሁን ለጀርመኑ የፋሺዝም መነሾ አንደኛው ምክንያት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክ ፖሊሲ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።  ከዚህ ዐይነቱ ትምህርት በመቅሰም ነው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት፣ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተገደዱት።

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በነፃ ገበያ ስም በካፒታሊስት አገሮችና፣ በአጠቃላይ አነጋገር ሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች መሀከል ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በይዘትም ሆነ  የላይ ላዩን ስንመለከት የተለያየ መሆኑን እንገነዘባለን። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ ኢኮኖሚያቸው የተከሰከሰው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ ኢኮኖሚያቸውን የገነቡት በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም። እነዚህ አገሮችም ሆነ፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያና የስካንዲኔቪያን አገሮች ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ግን ደግሞ ግለሰብ ካፒታሊስቶችን የማይጎዳና የማይቀናቀን ፖሊሲ በመከተላቸውና ተግባራዊ በማድረጋቸ ነው። ሰለሆነም በእነዚህ አገሮች በሙሉ መንግስታት ብቃትነት ያለው ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚያመች የትምህርት ተቋም በማስፋፋት፣ ርካሽ ብድር በማቅረብ፣ ግለሰብ ሀብታሞች ሊሳተፉ በማይችሉበት የኢኮኖሚ ዘርፎች፣ የመንገድና የመመላለሻ መስክ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍና በመደጎምም ሆነ ፖሊሲ በማውጣት ወደ ውስጥ ስፋ ያለ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ በዘመኑ አነጋገር የገበያ ኢኮኖሚ፣ በሳይንሱ ደግሞ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲገነባ አድርገውል። በእንደዚህ ዐይነቱ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ብድር ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል በመሆን፣ መንግስት፣ የግል ኩባንያዎች እንደየደረጃቸውና ቤተሰቦችም(House Holds) ገንዘብ ከባንኮች በመበደር ለመዋዕለ-ነዋይና ለፍጆታ በማዋል ለኢኮኖሚው ዕድገት ዕምርታ ሊሰጡት ችለዋል።  ስለሆነም በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ጊዜ፣ የኢኮኖሚው ዕድገት እያንዳንዱ ቤተሰብ በነፍስ ወከፍ በሚያገኘው ዐመታዊ ገቢ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣  የሳይንስና የቴክኖሎጂን ሚና፣ የረዠምና የአጭር ጊዜ ህይወት ያላቸውን የፍጆታ ዕቃዎች ምርትና አጠቃቀም፣ የከተማዎች ግንባታ፣ የመንገድና የመመላለሻ ጉዳይ፣ የመብራትና የንጹህ ውሃ አቅርቦት ጉዳይ፣ ሰፋ ያለ ገበያና የስራ ክፍፍል፣ ወዘተ.. ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ተጠቃለው በመታየት ነው ስለ አኮኖሚ ዕድገት መናገር የሚቻለው። በሌላ አነጋገር የነፍስ ወከፍ ገቢ ማደጉ ብቻ በራሱ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የአንድን አገር ዕድገትም በነፍስ ወከፍ ገቢ ብቻ ሊገለጽ  አይችልም።

የካፒታሊስትን ስርዓት ለየት የሚያደርገው ላይ ላዩን ሲታይ ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ የሚደረግበት ቢመስልም፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሁሉ ትግል የሚያካሂዱበትና በመንግስትም ላይ ጫና የሚያደርጉበት ሁኔታ በግልጽ ይታያል። በተለይም እንደዚህ ዐይነቱን የተለያየ አመለካከት ማስተጋባትና ትግል ማድረግ በስድሳኛውና በሰባኛው ዐመተ ምህረት የተለመደና የተጧጧፈ ነበር። በመሆኑም የማርክስ ዳስ ካፒታልና የኬይንስ ቲዎሪ በመስፋፋት ኒዎ-ሊበራሊዝም በአሸናፊነት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። የሰራተኛው ሙያ ማህበራትም የየራሳቸውን የምርምር ማዕከል እንዲከፈት በማድረግና ኢምፔሪካል ጥናት እንዲካሄድ በማድረግ ለደሞዝና ለማህበራዊ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ትግል ለማካሄድ ችለዋል። ዛሬም ቢሆን እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ትግል የሚደረግ ሲሆን፣ የደሞዝም ጭማሪ በአቅርቦትና በጠያቂ ህግ የሚደነገግ ሳይሆን፣ በድርድርና ከምርታማነትና ከዋጋ ግሽበት መጨመር ጋር እየተመዛዘነ ነው። በየዩኒቨርሲቲዎችም እንደኛ አገር አንድ ወጥ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ብቻ ሳይሆን የሚሰጠው፣ የተለያየ አመለካከትን በማነፃፀር ትምህርት ይሰጥና ትግልም ይደረጋል። ባለፉት ሃያ ዐመታት ደግሞ ኢኮኖሚክስን  ከፊዚክስና ከባይሎጂ ጋር በማያያዝ ግሩም ግሩም መጽሀፎችና ጥናቶች ይቀርባሉ። በተጨማሪም በ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ላይ የኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስ ቲዎሪ የሚባለው በአሜሪካን የህብረተሰብ ሳይንስ ምሁር  ቶርስታይን ቬብለን(Thorstein Veblen) የፈለቀውና የዳበረው ቲዎሪ በምሁሮች አስተሳተሰብና ለህብረተሰብ ትግል በሚያደርጉት አስተዋፅዖ ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ሊመጣ ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በእነ ማክስ ቬበርና በዱርክሃይም የዳበረው የሶስይሎጂ ዕውቀት በኢኮኖሚክ ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ በማድረግ የመንግስታትን አካሄድ እስከተወሰነ ደረጃ ይቆጣጠራል።

ወደ ተጨባጩ የህብረተሰብ ግንባታና ለውጥ ስንመጣ በሁለቱ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች እንደ ርዕዮተ-ዓለም የተወሰደውና አማራጭ የሌለው ተደርጎ የቀረበው የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል፣ ወይም ደግሞ የማክሮና የሚክሮ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ለዕድገት የቲዎሪ መሰረት የሆነበት የታሪክ ወቅት የለም። የፖለቲካ ኢኮኖሚ ቀሰ በቀስ መሰረት እየጣለ ከመጣ ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የአብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ የመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደነበረ ታሪክ ያረጋግጣል። የመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ፖሊሲም ተግባራዊ የሆነው አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ስነ-ስርዓት ባለው መልክ ከተማዎችን ከገነቡና ካዋቀሩ፣ የንግድና የዕድ-ጥበብ ስራ እንዲስፋፉ ሁኔታዎችን ካመቻቹ በኋላ ነው። ህብረ-ብሄሮች መቋቋም ሲጀምሩና የተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት አገሮቻቸውን ከውጭ ወረራ ለመከላከል ሲሉ የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ አጠቃላይ የህብረተሰብ ግንባታ ማካሄድ ተገደዱ። ምክንያቱም ከውስጥ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ህብረተሰብአዊ መተሳሰር እስከሌለ ድረስ በቀላሉ በውጭ ጠላት የሚጠቁ መሆናችውን በመገንዘባቸው ነው። በተለይም ጀርመን ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ድክመት ስለነበረባትና፣ በየጊዜውም የምትወረርና የምትጠቃ ስለነበረች፣ ከጥቃት ለመዳን የወሰደችው እርምጃ፣ በመጀመሪያ የክልል ፖለቲካን ማስወገድና የፊዩዳል ኃይሎችን ማዳከም ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ህዝቡን የሚያስተሳሰር በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባት ነው ብሄራዊ ነፃነቷን ማስከበር የቻለችው። ቀጥሎም የባቡር ሃዲድ በማስፋፋት በህዝቡ መሀከል ሊኖር የሚገባውን ግኑኝነትና የአንድነት ስሜት እንዲጠናከርና የብሄረተኝነት ስሜትም እንዲዳብር በማድረግ ለህብረ-ብሄር ምስረታ መንገዱን ቀደደች። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረተ-ሃሳብ እየተስፋፋ የመጣው። በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የእነ አዳም ስሚዙ የዌልዝ ኦፍ ኔሽን መጽሀፍ ተጽፎ ሲስፋፋ ዋና ዓላማው፣ በተለይም በውጭ ንግድ ላይ ርብርቦሽ በማድረግ፣ በአንድ በኩል በእንግሊዝ አገር እያደገ የመጣውን የከበርቴ መደብ ጥቅም ለመከላከልና ለማስጠበቅ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደ እንግሊዝ ያላደጉ አገሮችን ባሉበት ረግጠው እንዲቀሩ ለማድረግ ነበር። ይሁንና የአዳም ስሚዝ ቲዎሪ አበስትራክት በሆነ መልክ የቀረበና ከባላባቱ ስርዓት ወደ ካፒታሊዝም ስርዓት የተደረገውን ሽግግር ኢምፔሪካል በሆነ መልክ ያላቀረብ ትንተና ነው። በተጨማሪም ቀደም ብሎ በሃሳብ ደረጃ በሳይንስ ዓለም ውስጥ የተደረገውን ትግል ያላካተተ ነው። ስለሆነም የአዳም ስሚዙ ቲዎሪ የተጻፈው ካፒታሊዝም አንድ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ሲሆን፣ በተለይም በሬናሳንስ ዘመን የተደረገውን የመንፈስ ተሃድሶና የዕደ-ጥበብና የንግድ መስፋፋት፣ እንዲሁም የከተማዎች ግንባታ፣ ከዚያም በኋላ ደግሞ፣ ከፊዩዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ድረስ የተደረገውን ህብረተስብአዊ ሽግግርና፣ ውስጣዊ ቅራኔዎችና ትግሎች በፍጹም ያካተተ አይደለም። ስለዚህም ነው የማርክስ ካፒታል የተጨባጩን ሁኔታና የህብረተሰብ ትግል፣ እንዲሁም ካፒታሊዝም ደረጃ በደረጃ ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርትነት ወደ ተወሳሰበ የምርት ክንውንና የሀብት ከምችት፣ እንዲሁም በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ሁለቱ የኢኮኖሚ መስኮች፣ ማለትም የፍጆታን ዕቃ የሚያመርተው  የኢንዱስትሪ መስክና፣ በሌላ ወገን ደግሞ ማሺኖችንና ኢንዱስትሪዎችን የሚያመርተው ክፍል መተሳሰርና መደጋገፍ እንዳለ ሲያሳይ፣ ካፒታሊዝም ወይም የገበያ ኢኮኖሚ ካለነዚህ የሁለቱ ክፍሎች ሊያድግና አንድን አገር አዳርሶ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊኖረው እንዳማይችል ያመለከተው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በማርክስ ትንተና መሰረት ብድርና ውድድር ለካፒታሊዝም ዕድገት ዐይነተኛና ወሳኝ ሚና ሲጫወቱ፣ በዚህ አማካይነት ባንኮችና ኢንዱስትሪዎች እየተቆላለፉ በመምጣት ባንኮች የኢንዱስትሪዎችን ዕድገት ወደ መወሰን ደረጃ ያመራሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ የግዴታ የሀብት ክምችን በጥቂት ግለሰቦች እጅ ሲያጠናክር፣ ጥቂት ኦሊጎሎፖሊስቶች ወይም አቅራቢዎችና አምራቾች የገበያውንና የሰውን ህይወት ወደ መወሰን ያመራሉ። ስለሆነም ነፃ ገበያ መሆኑ ቀርቶ ኢኮኖሚው በጥቂት አገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች የሚወሰንና የሚደነገግ ይሆናል ማለት ነው። ተጨባጭ ሁኔታውም የሚያሳየው ይህንን ነው። በሌላ በኩል ለብዙዎቻችን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያለ ቢመስልም እዚያው በዚያው የገበያ ኢኮኖሚ በብዙ ሚሊዮን ህጎች የተተበተበ እንደሆነ እንመለከታለን። ስለዚህም ስለ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በምናወራበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ማለት ነው።

በመሆኑም ሰለ ኢኮኖሚክስ በሚወራበት ጊዜ አንድ ዐይነት አመለካከት ያላቻው ኢኮኖሚስቶች በዓለም ላይ እንደሌሉና ሊኖሩም እንደማይችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። የህብረተሰብ ሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ የርዕዮተ-ዓለም ትግል የሚካሄድበት መድረከ ስለሆነ በተለያየ አስተሳሰብ የተከፋፈለ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ከጥንቱ የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ለመረዳትና ለመተንተን የተለያዩ የአመለካከት ግንዛቤዎች በመዳበራቸው እነዚህ እንደ ሳይንሳዊ መመሪያዎች በመወሰድ እስከዛሬ ድረስ ሊዘልቁ ችለዋል። በተለይም ስልጣንን የጨበጡና ምሁራን ደጋፊዎቻቸው የሰፈነው ስርዓት ተቀባይነት(Ligitimacy) እንዲያገኝ ጠቅላላው ስርዓት በምን መልክ መተንተንና በኤሊቱም ጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ የአገዛዝ መሳሪያና መቆጣጠሪያ የሚሆን ልዩ ሳይንስ በማዳበር የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ መጠምዘዣ ሊሆን ችሏል። በመሆኑም በአውሮፓ ምድር ውስጥ በሃሳብ ደረጃና ጥቅምን በማስጠበቅ አኳያ የተካሄደውንና የሚካሄደውን የጦፈ ትግል ያልተከታተሉና የማይከታተሉ በዕውቀት ዘርፍና በምሁሮች ዘንድ አንድ ዐይነት አመለካከት ያለ ነው የሚመስላቸው። ተቀባይነት ካገኘው አሰታሰሰብ ወጣ ብሎ አንድ ነገር በሚጻፍበት ወይም በሚነገርበት ጊዜ ይህንን ዐይነቱን ለየት ያለ አመለካከት አይ እንደስድብ ይወስዱታል፣ ወይም ደግሞ እንደ ዕብድ አነጋገር አድርገው ይቆጥሩታል። ግልጽ መሆን ያለበት ነገር የአውሮፓው ዕድገት እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በክርክርና የተለያዩ አስተሳሰቦች በመጋጨታቸው ነው። ጭንቅላትም በዚህ ዐይነቱ የክርክር ዘዴና የተለያየ አመለካከት ሲፈተን መቻቻል ይመጣል። ወደ ኢኮኖሚክስም ስንመጣ ያለው ችግር በኢኮኖሚክስ የዕውቀት ሂደት ውስጥ የተደረገውን ትግል አብዛኛው የተከታተለው ስላልሆነና ፍላጎቱም ስለሌለ፣ ኢኮኖሚክስን እንደ አንድ ወጥ አስተሳሰብና በረቀቀ ዘዴ ብቻ ሊገለጽ የሚችል ዕውቀት ሆኖ ነው የሚወሰደው። በተለይም እንደኛ ባለው አገር ውስጥ  ዕውነተኛ ምሁራዊ ትግል ስለማይካሄድና ሀቁን ከውሸት ለመለየት ጥረትና ጥናት እንዲሁም ክርክር ስለማይደረግ፣ ኢኮኖሚክስ የተማሩቱን ሁሉ ኢኮኖሚስቶች እያሉ በመጥራት ህብረተሰብአዊ ችግር ፈቺዎች እንደሆኑ ማቅረብ የተለመደ ሆኗል። በተለይም የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ቲዎሪ እንደ እግዚአብሄር ቃል በሚወሰድበት ዓለምና አገር ውስጥ አፍን አውጥቶ ለመከራከር በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃም እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ የመሳሰሉት በዚህ ርዕዮተ-ዓለም ስለሚመሩና እነሱም እንደ አምላክ ስለሚታዩና ስለሚሰገድላቸው በየአገሮች ውስጥ መንግስታትን ለማሳሳትና ድህነትን ለመፈልፈል አመቺ ሁኔታን አግኝተዋል። በተለይም አሳሳች ኢኮኖሚስቶችን (Economic Hit Men) በመፍጠር መንግስታት በየአገሮቻቸው ውስጥ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥር የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳይከተሉና አገሮቻቸውንም አንዳይገነቡ ለማድረግ በቅተዋል።

ሌላው እጅግ አደገኛው የኢኮኖሚስቶች አምባገነንነት፣ ሌሎች ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት እንዲሁም ለጭንቅላትና ለህብረተስብ ተሃድሶ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ፊዚክስ፣ ማቲማቲክስ፣ ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፍልስፍናና ሌሎችን ዕውቀቶች በመግፋትና፣ የመንግስታትም አስተሳሰብ በነፃ ንግድና በገበያ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ አገሮችን ማፈራረስ ነው። ከዚህ ስንነሳ በተለይም ባለፉት ስድሳ ዐመታት በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የተጻፈውና እንደመመሪያ የተወሰደው ትምህርትና ፖሊሲ የበላይነትን በመቀዳጀት ብዙ የአፍሪካ አገሮች ወደ ውስጥ ያተኮረና የተወሳሰበ፣ እንዲሁም ድህነትን የሚቀርፍና  በሁለት እግሮቻቸው ቆመው ጠንካራ አገር እንዳይገነቡ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማስገደድ ስርዓተ-አልባ ሁኔታ ሊፈጠርና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ተፈጥሮአዊ መብታቸው እንዲገፈፍ ተደገርዋል። በዚህም ምክንያት ብዙ የአፍሪካ መንግስታትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ተፈጥሮ የለገሳቸውን ሀብት በስነ-ስርዓት ለመጠቀም ባለመቻላቸው በተለይም ወጣቱ ባልባሌ ቦታ እንዲውል ሲገደድ፣ የቻለው ደግሞ ወደ ውጭ በመሰደድ አዲስ ህይወት ለመገንባት የተገደደበትን ሁኔታ እንመለከታለን።  ከዚህ ስንነሳ ኢኮኖሚክስ ትርጉም እንዲኖረው ከተፈለገ 1ኛ) ከርዕዮተ-ዓለምና ከረቀቀ አስተሳሰብ መጽዳት አለበት፤ ይህም ማለት በምድር ላይ የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎችንና የኃይል አሰላለፎችን ለማንበብና ለመተንተን የሚያስችል ቲዎሪ ሆኖ መዘጋጀት አለበት። 2ኛ) ለህብረተሰብአዊ ዕድገት እንዲያመች ሆኖ መጻፍ አለበት። 3ኛ) የግዴታ ከፊዚክስና ከሌሎች የተፈጥሮ ሳይንስ ዕውቀቶች ጋር በመያያዝ ወሳኝ ሳይሆን ደጋፊ ዕወቀት ሆኖ መዘጋጀት አለበት። 4ኛ) የአንድን ህብረተሰብ ችግር መፍቻ መሳሪያ መሆን አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ነው በኔዎ-ሊበራል አቀንቃኚዎችና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰበከውንና የሚካሄደውን ግፊት መዋጋት የሚቻለው። ይህም ማለት ዕውነተኛ ህብረተስብአዊ ሀብት እንዲፈጠርና የተስተካከለ ዕድገትም እንዲመጣ ከተፈለገ ኢኮኖሚክስ ከፊዚክስ፣ ከማቲማቲክስ፣ ከባዮሎጂ፣ ከኬሚስትሪ፣ ከሶስይሎጂና ከፍልስፍና ዕውቀቶች ጋር መጣመር አለበት። ከዚህም በላይ የተለያዩ አመለካከቶች በንጽጽር መልክ በመቅረብ ተማሪው እንዲረዳው ያስፈልጋል። ምክንያቱም አንድ ዐይነት አመለካከት የበላይነትን በያዘበት ሁኔታ ውስጥ ሀቁን ከውሸት ለመለየት ማስቸገሩ ብቻ ሳይሆን፣ የበላይነትን የተቀዳጀው አስተሳሰብ ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ ለህብረተሰብአዊ ውዝግብ አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ነው።

ኢኮኖሚክስ መመለስ ያለባቸው ነገሮች !

አብዛኛውን ጊዜ ስለ ኢኮኖሚክስ በሚወራበት ጊዜ እንደ አበስትራክት ነገርና የሰውን ልጅ ፍላጎት ከማሟላትና አገርን ለመገንባት ከሚያደርገው አስተዋፅዖ ጋር በማያያዝ ሳይሆን፣ የነፃ ገበያን ወይም የነፃ ንግድን በማጋነንና በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ሰው ሁሉ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢሳተፍ ጥቅሙን ሊያሳድግ ይችላል ከሚለው  ተራ ግምት፣  ግን ደግሞ ሳይንሳዊና ታሪካዊ ካልሆነ ሁኔታ በመነሳት ነው። ስለሆነም የእያንዳንዱ ግለሰብ ፍላጎት ጥቅሙን ከፍ ለማድረግ መሯሯጥ ብቻ እንጂ ለመንፈሱ መጎልበስና እንደ አንድ ነፃ ዜጋና ሰው  የሚያደርጉት ማቴሪያላዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮች ላይ አትኩሮ መስጠት የለበትም ወደ ሚለው ሁኔታ ያመራናል። በመሆኑም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ሰው በፍጆታ የሚገለጸውን ፍላጎቱን ሊያሟላ የሚችለው በገበያ አማካይነት ብቻ ሲሆን፣ ይህንን ፍላጎቱን ለማሟላት ደግሞ የግዴታ ገንዘብ እንዲኖረው ያስፈልጋል።  ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ተቀጥሮ መስራት አለበት፤ ካሊያም በአንዳች መንገድ ገንዘብ ለማግኝት ሲል መሯሯጥ አለበት። በእንደዚህ ዐይነቱ አበስትራክት አስተሳሰብ ውስጥ የሀብት ቁጥጥርና ክፍፍል፣ የፖለቲካና የህብረተሰብ አወቃቀር ቦታ የላቸውም። ሁሉም የተሰጡና መስተካከልም የሚገባቸው አይደሉም። መስተካከል ካለባቸው ደግሞ መንግስት እጁን ከኢኮኖሚ ውስጥ በማውጣትና በሱ ቁጥጥር ስር ያሉትን የህዝብ ሀብቶች ሁሉ በመሸጥ ሁሉም ነገር ‘በገበያ ህግ’ እንዲካሄድ የሚያደርግ ከሆነ እያንዳንዱ በገበያ ላይ የሚሳተፍ ሁሉ እንደየ አስተዋፅዖው የድርሻውን ያገኛል ይላል።  ፍላጎቱንም ሊያሙላ የሚችለውም በዚህ አማካይነት ብቻ ነው።

ይሁንና ግን በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥና ኢኮኖሚም እንደ አንድ ዘርፍ ዕውቀት መወሰድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ  ሰለ ኢኮኖሚክ እኩልነትና፣(Economic Jutice) በኋላ ደግሞ የኢኮኖሚክስ የመጀመሪያው መሰረተ-ሃሳብ የሰውን ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላትና ህብረተሰብአዊ ግጭት እንዳይኖር ሚዛናዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል ነው የሚለው ዋናው የመከራከሪያ ነጥብ ሆኗል። በተለይም በእንግሊዙ የኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት የደረሰውን ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልና ድህነት ተዘዋውረው ያጠኑት የጀርመን ሁለ-ገብ ምሁራን አትኩሮ የሰጡት የኢኮኖሚክስ ዋናው መሰረተ ሃሳብ የማህበራዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ነው የሚል ነው። በመሆኑም ምግብ፣ ንጹህ ውሃ፣ መጠለያና ትምህርት እንዲሁም ደግሞ መቀቀያና ማሞቂያ ተቀዳሚዎቹና መሟላትም ያለባቸው ናቸው ብለው በማንሳትና በማስተማር ነው በመንግስታቸው ላይ ጫና ያደርጉ የነበረው። በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ፣ በጊዜው የነበረውን ኋላ-ቀርነትንና ድህነትን ለመቅረፍና ለማስወገድ የሚቻለው ሁለ-ገብ ትምህርት በማስፋፋትና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ብቻ ነው የሚል ግልጽ አመለካከትና ርዕይ ነበራቸው። ዓላማቸውም በዚህ አማካይነት ጠንካራ ህብረ-ብሄር ለመመስረት የሚያስቸለውን መሰረት በመጣል ወደ አገር ግንባታ መሸገጋር ነበር። በዚህ ዐይነቱ የአገር ግንባታ ውስጥ ኢኮኖሚክስ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተለይም በኢንጂነሪንግ ስር በመሆን፣  ወሳኝ ሳይሆን ደጋፊ ዕውቀት በመሆንና ከሌሎች ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ህብረተሰብአዊ ሀብት መፍጠሪያ መሳሪያ ሊሆን ችሏል። በተለይም እንደ መካኒካል ኢንጂነሪግ የመሳሰሉት ዕውቀቶችና የትምህርት ዘርፎች ወሳኝ ሚናን በመጫወት ዋናው የሀብት ማፈለቂያና ማዳበሪያ መሳሪያዎች በመሆን የኢንዱስትሪ አብዮትን ማፋጠን ችለዋል።

ስለሆነም ኢኮኖሚክስ ከሌሎች ነገሮች ተነጥሎ የሚታይና በማቲማቲክስ በማሸብረቅ ጥቂቶች የሚዝናኑበትና ሰውን የሚያወናብዱበት መሳራያ ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴኮኖሎጂ በመደገፍ ሰፋ ያለና ጠንካራ፣ እንዲሁም ደግሞ ስርዓት ያለው አገር መገንባት የሚያስችል ዕውቀት በመሆን  ቀደም ብለውም ሆነ በኋላ  በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን  ብቅ ባሉ ምሁራን ሊዳብር ችሏል። በመሆኑም ኢኮኖሚክስ ከሌሎች ነገሮች ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን፣ የዕውቀት አንድ ዘርፍ በመሆን፣ በምን መልክ በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጽ ዕውነተኛ ህዝባዊ ሀብት ሊፈጠር ይችላል? የኢኮኖሚክስስ ሚና ምን ሊሆን ይችላል?  በሚለው ዙሪያ  ከፍተኛ ክርክር ይደረግ ነበር። ከዚህም በመነሳት ነው ከተማዎችና መንደሮች፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ የገበያ አዳራሾችና መዝናኛዎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ከረዝም ጊዜ አንፃር ደግሞ የውሃ ማስገቢያዎችና የቆሻሻ ውሃ ፍሳሽ ማፍሰሻዎች የተሰሩትና፣ ቀስ በቀስም በሙከራና በልምድ ዛሬ የምናየውና የምንኖርበት ደረጃ ላይ ሊደረሱ የተቻሉት። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ቀደም ብሎ የተጀመረና ሁሉም ምሁራን በቲዎሪ ብቻ ሳወሰኑ በተግባርም በመመንዘር በመጀመሪያ ለአገዛዞች ሳይሆን ህዝብን ከድህነት ማውጣት አለብን የሚለውን አስተሳሰብ በጭንቅላታቸው ውስጥ በመቅረጽ ነው ለአውሮፓው ስልጣኔ መንገዱን የቀደዱት። ዛሬ የምንጠቀምባቸው ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ከአራትና ከአምስት መቶ ዐመታት በፊት የተዘጋጁ ናቸው። የካፒታሊዝም ስርዓት ቴክኖሎጂን ለራሱ ትርፍ ማካባቻ ከማድረጉ በፊት በሳይንቲስቶችና በፈላስፋዎች ዘንድ የነበረው ዕምነትና ስምምነት የሰውን ልጅ ከጨለማ ውስጥ አውጥቶ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በተፈጥሮ ላይ የበላይነትን እንዲቀዳጅና ኑሮውን እንዲያሻሽል ነው። ጋሊሊዮም ሆነ ኬፕለር፣ እንዲሁም ኒውተንና ላይብኒዝ የሳይንስ ግኝታቸውን በምንም ዐይነት ለሰው ልጅ መጨቆኛና ተፈጥሮን መበዝበዣ መሳሪያዎች እንዲሆኑ አድርገው አይደለም የፈጠሩት። ያም ሆነ ይህ ሳይንሳዊ ግኝትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠርና ተግባራዊ መሆንና ለሰው ልጁ የሚጠቅሙ ማንኛውንም ነገሮች ማምረት የዕድገት ዋናው ቁልፍ መሳሪያዎች ቢሆኑም፣  እንደዚሁ ዐይነቱ ዕድገት ከአጠቃላዩ የህብረተሰብ ለውጥና(Social Transformation) የኑሮ መሻሻል ሁኔታ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።

ለእንደዚህ ዐይነቱ ዕድገት የግዴታ በየአገሮች ውስጥ  በደንብ የተደራጀ የሰራ ክፍፍል መኖር ሲገባው ፣ በተለያዩ መስኮች መሀከል በሚደረገው መደጋገፍና መያያዝ፣ የምርት ሂደት መጠናከርና በጥራትም ሆነ በብዛት ገበያ ላይ መቅረብ ለኢኮኖሚው ዕድገት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ከፍተኛ ግንዛቤና ግልጽ አቋም እንደነበር መረዳት ይቻላል። የኢኮኖሚ ዋናው መሰረታዊ ጥያቄም በረቀቀ መልክ የመቅረቡ ጉዳይ ሳይሆን ፣ በምድር ላይ አፍጦ አግጦ የሚታዩ ችግሮችን መፍቺያና፣ አንድን አገር ገንብቶ ህዝብ በደስታ የሚኖርበትን ሰላማዊ ሁኔታን መፍጥር መሆኑን በግልጽ የተቀመጠ መሰረተ-ሃሳብ ነው ። ስለሆነም ይህንን የተቃና አስተሳሰብ የሚያሳስትና ድህነትን የሚፈለፍለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መቃወምና መታገል ዋናው ተግባራቸው ነበር። ለዚህም ነው በተለይም የጀርመን ፈላስፎችና  በጊዜው የአዳም ስሚዝን የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ አጥበቀው መዋጋት የጀመሩት አንዳንድ የኢኮኖሚክስ ተመራማሪዎች የራሳቸውን ቲዎሪ ማፍለቅና ማዳባር የተያያዙት። የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውም ከማህበራዊና ከህብረተሰብ ግንባታ ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን፣ ጥበባዊ ባህርይ ያለውና የሰውን መንፈስ እንዲሰበስብ ሆኖ ነው ተግባራዊ ይደረግ የነበረው። የፖሊሲውም ዋና መሰረተ-ሃሳብ ገንዘብ በማግኘት መዝናናት ሳይሆን፣ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትና እሴት መፍጠር ነበር። አነሳሳቸውና እንቅስቃሴያቸውም ሰፋ ያለ ምሁራዊ መሰረት ያለው ህብረተሰብ መፍጠር ሲሆን፣ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጠር የሚችለው በንግድ አማካይነት ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ እንደሆነ ከፍተኛ ግንዛቤ ነበር። በተግባርም ያሳዩት ይህንን ነው።

ያም ሆነ ይህ በታሪክ ውስጥ በአጠቃላይ ስለ ኢኮኖሚክስ ምንንነትና፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ስለሚኖረው ሚና ክርክር ሲደረግ በመጀመሪያ ደረጃ ኢኮኖሚክስ በራሱ ብቻ አንድን ነገር ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ነገር ሊለወጥ እንደማይችል ከፍተኛ ግንዛቤ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ከመዳበሩ በፊት፣ በፈላስፋዎችና በሳይንቲስቶች ዘንድ የነበረው ስምምነት ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ካለሳይንሳዊ ግኝትና ካለቴክኖሎጂ በፍጹም ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችልና፣ ማንኛውንም ለሰው ልጅ  አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በጥራትም ሆነ በተለያየ መልክ ማምረት የሚቻለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ እንደሆነ ነው። ለዚህም ነው ከአስራ አምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ብቅ ያሉት ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች በሳይንሳዊ ግኝት ላይ በመረባረብ የተፈጥሮን ውስጣዊ ህግ ለመረዳት ይጥሩ የነበረው። ከዚህም በመነሳት ከመካኒክስ በማለፍ ቀስ በቀስ ወደ ተወሳሰበ ግኝት በመሸጋገር በሰው ልጅ ዕድገት ውስጥ ኃይል(Energy) ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ለማረጋገጥ የቻሉት። በመጀመሪያ፣ ማንኛውንም የምርት ማምረቻ መሳሪያ ለመፍጠር ምርምር ዋናው መሰረተ ሃሳብ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በኃይል አማካይነት ብቻ የምርት መሳሪያንም ለማምረትና አንድን ጥሬ ነገር ወደ ሌላ ነገር በመለወጥ ህብረተሰብአዊ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል ከፍተኛ ግንዛቤ ሊደረስበት የተቻለው። ስለሆነም በኢኮኖሚ ክንዋኔና ዕድገት ውስጥ እነ አዳም ስሚዝ እንደሚሉት ሳይሆን መሬት(Land)፣ ካፒታልና(Capital)፣ የሰው ጉልበት በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ዋና የምርት ማምረቻ ኃይሎች መታየት ያለባቸው፣ የማሰብ ኃይል፣ ታታሪነት፣ ኃይልና ማሺን ዋናዎች የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኃይሎችና መሰረቶች እንደሆኑ ግልጽ በሆነ መልክ በመቀመጥ ከፍተኛ ግንዛቤ የተደረሰበት። ስለሆነም በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሂደትና ዕድገት ውስጥ ብዝበዛ ዐይነተኛ ሚናን ቢጫወትም፣ ዕውነተኛ  ዕድገት ሊመጣ የቻለውና የሚችለው ተከታታይነት ያለው የቴክኖሎጂ ፈጠራና የኃይል ማመንጫ በየጊዜው እየዳበሩ የመጡ እንደሆን ብቻ መሆኑ የታወቀ ነበር። ለምሳሌ የኃይልን ጉዳይ ስንመለከት፣ እስከ አስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች እንጨት ዋናው የኃይል ማመንጫ ዘዴ ሲሆን፣ ዛፎች እየወደሙ ሲሄዱና የኃይልም ዕጥረት ሲከሰት በአጋጣሚ የዲንጋይ ከሰልን በማግኘት ይህ ዐይነቱ አዲስ የኃይል ማመንጫ ዘዴ ለኢንዱስትሪ አብዮት ተግባራዊነት ከፍተኛ ሚናን በመጫወት የካፒታሊዝምን ዕድገት ዕምርታ ሊሰጠው ችሏል። ከዚያም በኋላ የኒውክላር ኢነርጂ፣ እንዲሁም ዘይትና ጋዝ በመካተት የኢንዱስትሪ ካፒታሊዝምን የተወሳሰበ ዕድገት ማፋጠን ችለዋል። ዛሬ ደግሞ እንደ ፀሀይ፣ ነፋስና የኦርጋኒክ ኃይል ማመንጫዎች(Regenerative Energy) ከፍተኛ ምርምር የሚደረግባቸው የዕድገት አጋዦች በመሆን፣ ለአካባቢም ደህንነት አስፈላጊ መሆናቸውን በመረዳት ግልጽ በሆነ መልክ በህግ በመደንገግ መንግስታዊና ህዝባዊ ድጋፍ እያገኙ የመጡ  የኃይል ማመንጫ ዘዴዎች ናቸው።

ስለሆነም  በመጀመሪያ ደረጃ ኢኮኖሚ መመለስ ስለሚገባው ጥያቄዎች ሲወራ፣ የኢኮኖሚን ትርጉም ይበልጥ ለመረዳት ከተፈለገ መሰረታዊ ፍላጎቶችና ከማሟላት ተሻግሮ መሄድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ሊሟሉ የሚችሉት ተከታታይነት ያለው የቴክኖሎጂ ምርምር ሲኖርና የኃይል ማመንጫም ሲዳብርና ሲስፋፋ ብቻ ነው። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በቁጥር እየጨመረ ስለሚሄድ የግዴታ ይህንን በቁጥር እያደገ የሚሄድ ህዝብ መመገብ የሚቻለው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩና፣ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች የሚያግዙ ብቃትነት ያላቸው የኃይል ማመንጫዎች ሲገነቡና ሲዳብሩ ብቻ ነው። እንደ ቴክኖሎጂም የኃይል ማመንጫ ዘዴ በአገር ውስጥ መዳበር ያለበት ሲሆን፣ የግዴታ ከአንድ የኃይል ማመንጫ ወደ ሌላ የኃይል ማመንጫና አጠቃቀም ዘዴ መሸጋገርና፣ የኃይል ማመንጫዎችንም በአንድ ነገር ላይ ብቻ እንዳይመካ ማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት  ከረዠም ጊዜ ጀምሮ ስምምነተ የተደረሰበትና በተግባርም የተረጋገጠ ነው።

ወደ ሁሉቱ ኢሳት ቴሌቪዠን ላይ ቀርበው የተጋበዙት የኢኮኖሚስት „ጠበብተኞችም“ ሆነ ጠያቂው ጋዜጠኛ የኢኮኖሚክስን ትርጉም ድህነትን ለመቅረፍ ስለሚኖረው ሚናና በአገር ግንባታ ላይ የሚኖረውን ከፈተኛ አስተዋፅዖ በማንሳት መወያየት ሳይሆን፣ የተከታተለውንና ያዳመጠውን ግራ የሚያጋባ አቀራረብ ነበር ማለት ይቻላል። ኢኮኖሚክስ ማሟላት ስላለበት መሰረታዊ ነገሮች(Basic Needs) ሰፋ ያለ ውይይት በመክፈትና ከማስተማር ይልቅ፣ አበስትራክት በሆነ ነገር ላይ በመረባረብ ጊዜ ሊባክን ችሏል። የዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ችግር ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ኢኮኖሚክስ በረቀቀ መልክ(Abestract) ስለሚሰጥ ኢኮኖሚስቶች የሚሆኑና የማይሆኑ፣ ህዝብ የማይገባውን የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳቦች የሚሏቸውን እንደ ኦፖርቹኒቲ ኮስት ወይም አማራጭ ዋጋ፣ ሰብስቲቱሽን ወይም መተካት፣ ትራንስፎርሜሽን ከርብ ወይም ሪሶርሶን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላኛው ላይ በማሸጋገር በአንድ ነገር ላይ ብቻ በመረባረብ ለዓለም ገበያ ምርት ማቅረብ፣ ዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍል፣ ተመሳሳይ ጥቅምን የሚሰጡና ከተጠቃሚው አንፃር አማራጭ ሊሆኑ የማይችሉ ምርቶች(Indifference Curve) ወይም ደግሞ ተጠቃሚው የፈለገውን ገዝቶ ቢጠቀም ጉዳዩ እንዳይደለ በመሳሰሉት፣ በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ረቀው የቀረቡት ፅንሰ-ሃሳቦች በመስፋፋታቸውና እነዚህ የኢኮኖሚክስ መሰረታዊ ሃሳቦች ተደርገው በመወሰዳቸው ዕውነተኛው የኢኮኖሚክስ ትርጉም ሊዛባ ችሏል። ታዳጊውንም ወጣት በዚህ በመመረዝ የኢኮኖሚክስን መሰረታዊ ዓላማና ሚና እንዳይረዳ ሊያደርጉት በቅተዋል።

እንደገና ወደ ሁለቱ በኢሳት ቴሌቪዠን ላይ ወደ ተጋበዙት ኢኮኖሚስቶች ጋ ስመጣ በመሰረቱ ያላቸው አመለካከት የማያስታርቅ አመለካከት ሳይሆን፣ በመንግስት ጣልቃ ገብነትና ጣልቃ አለመግባት ላይ ብቻ ያላቸው ልዩነት ነው። በተጨማሪም በሁለቱ መሀከል ዛሬ አደገ በሚባለው ኢኮኖሚ ላይ መሰረታዊ የሆነ ልዩነት ያላቸው ሳይሆን፣ በሚታዩ ነገሮች ላይ በማትኮር ብቻ የተደረሰበት ልዩነት እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሁለቱም ኢኮኖሚስቶች ተጨባጩን ሁኔታ „በተለያየ ዐይን“ ቢመለከቱም በይዘት ግን ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። ይሁንና ሁለቱም ኢኮኖሚስቶች በቲዎሪ ደረጃም ሆነ በሳይንሳዊ መለኪያ የደረሱበትን ውጤት ማረጋገጥ አልቻሉም። ለምሳሌ ድ/ር ዳንኤል „ድህነት ተስፋፍቷል፣ የኢኮኖሚው ዕድገት ጥቂቶችን ብቻ ነው የጠቀመው“፣ ሲል ለምን ይህ ዐይነቱ ሁኔታ እንደተከሰተ ምክንያቶችን ሊያብራራና ለአድማጩ ሊያስረዳ በፍጹም አልቻለም። ዶ/ር ፀሀይ ደግሞ „የኢኮኖሚ ዕድገት አለ“ ሲል ዕድገቱ በምን ላይ እንደተመረኮዘና፣ ይህ ዐይነቱ ዕድገት ዘላቂነት ይኑረው አይኑረው፣ አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ሀብት ለመፍጠር ኃይል ይኑረው አይኑረው፣ በፍጹም ማሳየት አልቻለም። እንዲያው በደፈናው መንግስት በአሃዝ መልክ የሚያቀርበውን መረጃም ሆነ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚያቀርቡትን ስሌቶች „ካላመን ማንን ነው ታዲያ ልናምን የምንችለው“? በማለት ከሳይንስና ከተጫባጩ ሁኔታ ጋር በፍጹም የማይጣጣሙ ነገሮች ሲነግረን ነበር። በእሱም ዕምነት፣ አፍጦ አግጦ የሚታየው ድህነት፣ በብዛት የቆሻሻ መኖሪያዎች መስፋፋት፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ከቆሻሻ ቦታ ምግብ እየፈለገ መብላት፣ በልመና መተዳደር፣ ስራ አጥቶ መንቀዋለል፣ የጭአት ቤቶች ልክ እንደ ቡና ቤቶች መስፋፋት፣ የሴተኛ አዳሪ መስፋፋት፣ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣት አገሩ ውስጥ የመማርና የመስራት ዕድል ለማግኘት ባለመቻሉ መሰደድ፣ የከተማዎች የሁለተኛ ዕቃ መጣያና ወደ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን መለወጣቸው ሳይሆን፣ ዋናው የኢኮኖሚ ዕድገቱ መለኪያ፣ እነዚህ እንደ አምላክ የሚቆጠሩት ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖችና መንግስት የሚሰጡት ቁጥሮች ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በወያኔ ካድሬዎችና በመጤ ከበርቴዎች በከተማ ውስጥ፣ በተለይም አዲስ አበባ ቦታዎችን ለልማት እንፈልጋቸዋለን እየተባለ ህዝቡ ከቦታው በመፈናቀል ለጅብና ለብርድ የታደረገበትንና ራሱንም እንዲገድል የተደረገበት ሁኔታ፣ ይህ ሁሉ የዕድገት መለኪያው ነው። ልክ እንደ ወያኔ መሪዎችና ካድሬዎቻቸው የዕድገት መለኪያዎች የሚሰሩትና የሚታዩት ህንፃዎች እንጂ የህዝቡ የኑሮ መሻሻል አይደለም። በዶ/ር ፀሀይ ዕምነት አንድ ህዝብ ተጨባጭ ነገር የሚበላና የሚጠጣ ሳይሆን፣ ሊመገብና ሊጠጣ የሚችለው ቁጥርንና ሊኖረም የሚችለው በቁጥር ዓለም ውስጥ ብቻ ነው። ስለዚህም የሰው ልጅ ዋናው ፍላጎቱ በቁጥር ሊገለጽ የሚችል እንጂ፣ ኑሮውን በማሻሻልና አዲስ ህይወት በመገንባት ማቴሪያላዊና መንፈሳዊ ደስታን የሚጎናጸፍበት አይደለም። በመሆኑም ለአንድ አገር ዕድገት ዋናው ቁም ነገር ቁጥር መታየቱ እንጂ የሰው ልጅ ኑሮ መሻሻሉ አይደለም የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያው። ፈላስፋዎች እንደዚህ ዐይነቱን አስተሳሰብና ዕውቀት በጭንቅላቱ የቆመ ይሉታል።

በሌላ ወገን ዶ/ር ዳንኤል ያነሳው የድህነት መስፋፋቱና የኢኮኖሚው አለማደግ ጉዳይ አስፈላጊ የሆነውን ያህል የሱ ችግር ባለፉት ሃያ  ሶስት ዐመታት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክና በአጭሩ የዓለም ኮሙኒቲ እየተባለ በሚጠራው አማካይነት ተግባራዊ የሆነውን የነፃ ገበያ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዛሬ ለተስፋፋው ድህነትና፣ ለከተማዎች መዝረክረክና ለቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች መስፋፋት ተጠያቂ ለማድረግ አለመቻሉ፣ ወይም ደግሞ ለመመርመር ያለመሞከሩ ነው። የሱ ዋና ችግርና ክስ አሁንም ቢሆን መሬት ጉልታዊነት አለው ብሎ ሲያምን፣ ባጠቃላይ ሲታይ ኢኮኖሚው በነፃ ገበያ መርሆች ላይ የሚራመድ አይደለም የሚል ነው። ይህ ዐይነቱ የተዛባ አቀራረብ የነገሮችን ሂደት ደረጃ በደረጃ እንዳናይና ወደ ውስጥ ገብተን እንዳንመረምር ያግደናል። ሌላው አሳሳች አካሄድ ደግሞ፣ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በዚህ የድህነት ፍልፍላ ሂደት ውስጥ እጁን አላስገባም፤ ለሃያሶስት ዐመታት በአገራችን ምድር የተካሄደው ፖሊሲ ራሱ ወያኔ በዕውቅ የነደፈውና ተግባራዊ ያደረገው ነው ወደ ሚለው እጅግ ወደ ተሳሳሰተ ውሳኔ እንድናመራ ይዳርገናል። በዚህም መሰረት የችግሩን ዋና ምንጭና አንድ አካል የሆነውን እንዳንረዳና መፍትሄ እንዳንፈልግ ያግደናል።

ለመሆኑ ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ ከጥቂት ዐመታት በኋላ ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ማካሄድ የጀመረው ? ለምንስ ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዛሬ በአገራችን ምድር ለተስፋፋው ድህነትና ለህዝባችን መድቀቅ ዋና ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። „በዓለም አፍ ኮሙኒቲውና“ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ የወታደራዊ አገዛዝ እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ በአገራችን የነበረው የኢኮኖሚ ስርዓት „ሶሻሊስታዊ“ ሲሆን፣ ፖሊሲውም „የዕዝ ኢኮኖሚ“ ነው የሚል ነበር። በመሆኑም ይሉናል እነዚህ  ምሁራን፣ በየጊዜው በኢትዮጵያ ምድር ለሚከሰተው ረሃብና ለተስፋፋው ድህነት የዕዝ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆኑና የሶሻሊስት ስርዓት በመስፈኑ ነው የሚል፣ ከተጨባጩና ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም አቋም ነበር ያስተጋቡ የነበረው። በመሰረቱ ከ1975 ዓ.ም እ.አ ጀምሮ በህዝብና በጊዜው በነበሩት ተራማጆች ግፊት የተነሳ ቀደም ብለው በጥቂት የውጭና የውስጥ ባለሀብቶች ስር የነበሩ ኩባንያዎችና መሬትንም ጨምሮ፣ ይሁንና ግን ደግሞ ከዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገትና ከህዝባዊ የሀብት ፈጠራ አንፃር ይህንንም ያህል አስተዋፅዖ ያላደረጉ በወታደራዊ አገዛዝ  በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደዋሉ የማይካድ ሀቅ ነው። ይህ መደረጉና አንዳንድ በመንግስት የተደገፉ ለህዝብ የሚጥቅሙ፣ እንደመሬት አዋጁ የመሳሰሉት ተግባራዊ በመሆናቸው የኢኮኖሚው ስርዓት ሶሻሊስታዊና ፖሊሲውም የዕዝ ነው የሚያሰኘው አንዳችም ነገር የለም። ሊሆንም አይችልም። በተለይም ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚቆጠር ህዝብ ከእጅ ወደ አፍ(Subsistence Economy) በሆነ የእርሻ ክንዋኔና ኢንፎርማል መስክ በተስፋፋበት አገር ኢኮኖሚውን ወደ ዕዝ ለመለወጥና የሶሻሊስት ስርዓት ለመመስረት በጣም ያስቸግራል። የዕዝ ኢኮኖሚ ዕቅድ ሰፋ ያለ የኢንዱስትሪ መስክና ብቃት ያለው የአደረጃጀት ሁኔታ ሲያስፈልገው፣ በተለይም ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ብቃት ያለው የሰው ኃይልና ኢንስቲቱሽን መኖር እጅግ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። በጊዜው  እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች በፍጹም አልነበሩም።  ስለሆነም ከዚህ ከኢትዮጵያ የተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም አስተሳሰብ በመንዛትና፣ ሶሻሊዝንም የጨለማ ስርዓት ምንጭ አድርጎ በመውሰድ ወያኔ ስልጣን ሊወጣ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል የቀረበለት ቅድመ-ሁኔታ የኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ ፖሊሲን ወይም የመዋቅር መስተካከያ ፕሮግራምን(Structural Adjustment Program) ተግባራዊ ማድረግ ነው። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር የልውውጥ ዋጋው እንዲቀንስ ማድረግ(Devaluation)፣ በመንግስት ቅጥጥር ስር የነበሩ የንግድ ኩባንያዎችንና ፋብሪካዎችን በሺያጭ ወደ ግል ማዘዋወር፣ በዋጋዎች ላይ የሚደረገውን ድጎማ ማንሳት፣ ወይንም ለገበያው ተዋንያን ልቅ ማድረግ፣ የውጭውን ንግድ ልቅ ማድረግ … ወዘተ. የሚሉ ናቸው። ከመሬቱ አዋጅ በስተቀር በእርግጥም እነዚህን ነገሮች አንድ በአንድ ተግባራዊ በማድረግ ወያኔ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ያቀረበለትን ትዕዛዝ ለመፈጸም በቃ። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ  የኢኮኖሚ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ባለመሆኑና፣ የችግሩንም ምንጭ ለማሳየት ያልቻለ በመሆኑ ወደ ተግባር በሚመነዘርበት ጊዜ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ „በቡሃ ላይ የጆሮ ደግፍ“  እንደሚባለው አነጋገር ወደ ባሰ ድህነት ውስጥ ነው የከተተን።

በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር እንዲቀንስ ቢደረግም እንደታመነበትና እንደተጠበቀው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በብዛት ጠያቂን በማግኘት የአገሪቱ ካዚና በዶላር ክምችት ሊጣበብ አልቻለም። ቡናና ሌሎች የጥሬ ሀብቶች በተመሳሳይ ጥራት በሌሎችም አገሮች ሰለሚቀርቡና፣ የዓለምም ገበያ ከሚፈልገው በላይ መግዛት ስለማይችል እንደተባለው ከቀድሞው ሁኔታ ጋር ሲወዳደር  በብዙ ሚሊዮን ቶን የሚገመት ቡናም ሆነ ሌሎች የጥሬ-ሀብቶችን መሸጥ አልተቻለም። በአንፃሩ ግን ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ቅነሳ ከውጭ የምርት መሳሪያዎችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን እያስገባ የሚያመርተውን ነጋዴና አምራች ኃይል ነው መጉዳት የጀመረው። ምክንያቱም ነጋዴውም ሆነ አምራቹ ከፖሊሲው ለውጥ በኋላ አንድ የአሜሪካን ዶላር ለመግዛት እንደበፊቱ ሁለት ብር ከአምስት ሳንቲም  ሳይሆን የግዴታ አምስት የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ ስለነበረበት ነው። ይህም ማለት አንድ ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ለሚፈልግ ሰው ከቀድሞው ሁኔታ ጋር ሲወዳደር እጥፍ የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ አለበት ማለት ነው።  በተከታታይ ዐመታት የብርና የዶላር ልውውጥ እየቀነሰ በመምጣቱ ሁኔታው እየተባባሰ ነው የመጣው። በመሆኑም አንድ ዶላር ለመግዛት በመጀመሪያው ወቅት አምስት የኢትዮጵያ ብር፣ ከዚያ በኋላ ድግሞ ወደ አስራስደስትና ሃያ የኢትዮጵያ ብር ለማቅረብ ያልቻለ  የተወሰነ ብር ብቻ በመለወጥና ዕቃዎችን በማስመጣት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን አንደቀድሞው ሳይሆን በቀዘቀዘ መልክ እንዲያካሂድ የተገደደበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በተግባርም የታየው ይህ ነው። ከዚህ ባሻገር ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ቅነሳ ፖሊሲ በዋጋ ግሽበት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር ችሏል። ወደ ግል ሀብትነት መዘዋወር አለባቸው የተባሉትንና የተሸጡትን ኩባንያዎችና የንግድ መደብሮች ስንመለከት በነፃ ገበያ መርሆች ላይ በአቅራቢና በጠያቂ መሰረት የተሸጡ ሳይሆን፣ ለወያኔዎችና ወይም ከሱ ጋር ቅርበት ላላቸው ድርጀቶችና እንደ አላሙዲን ለመሳሰሉት ግለሰቦች ነው በባንክ እየተደገፉ እንዲገዙ የተደረገው። በጊዜው እነዚህ ኩባንያዎች ወደ ግል ተዘዋውረዋል ሲባል ወደ 50 000 ሰራተኛ ከስራ መስኩ እንደተባረረ ተመዝግቧል። ከዚህ ባሻገር ወደ ግል የተዘዋወሩት ኩባንያዎችም ሆነ ኢንዱስትሪዎች ለፈጠራ ስራና ለተተከታታይ የመዋዕለ-ነዋይ የሚያመቹ ስላልነበሩ የቀድሞው ሁኔታ በሌላ መልኩ እንዲቀጥልና የኢኮኖሚው ውስጣዊ ድክመት(structural weakness) እንዲስፋፋና ጥልቀት እንዲኖረው ተደርጓል። በመሆኑም ኢንዱስትሪዎችን ገዛ የተባለው አዲሱ የወያኔ „ከበርቴና“፣ በወያኔ የሚደገፈው ዘራፊ ኃይል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል የስራ መስክ መክፈት የቻለ ሳይሆን፣ የሚቀናቀናውን ቀስ በቀስ  በሆነ ባልሆነ አሳቦ ከገበያው ተፈናጥሮ እንዲወጣ ማድረግን ነው የተያያዘው። በሌላ አነጋገር፣ ብዙ የተደሰኮረለት የገበያ ኢኮኖሚ ተወዳዳሪዎችን ያፈራና ነፃ የሆነ ሳይሆን፣ ጥቂቱን እንዲደልብ ያደረግና አገራችንን መሞከሪያ ያደረገ፣ ለዘረፋ ያመቸና ጥቂቶች ድግሞ ካለምንም ስራ ወደ ቱጃርነት እንዲለወጡ ያደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ወደ ክልሎች ስንሄድ ደግሞ „ነፃነታችንን ተቀዳጀን“ ያሉት የየክልሉ የጭቁን ብሄረሰብ „ተጠሪዎች“ ወደ ዘረፋና ለራስ ቤት ሰርቶ እንደ ንጉስ  መታየትና ቂም በቀል መወጣትን እንጂ፣ ሰፋ ያለ፣ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመረኮዘና፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊያካትት የሚችል ኢኮኖሚያዊ አንቅስቃሴ አይደለም ማካሄድ የጀመሩት። የነበራቸው ዕውቀትና ጭፍን አስተሳሰብ ስለማይፈቅድላቸው ነፃ እናወጣሃለን ያሉትን ጭቁን ህዝብ ነው ወደ መዝረፍና በሱ ላይ መዘባነን እንደፈሊጥ አድርገው የያዙት። የውጭውን ንግድም ስንመለከት ገበያው ልቅ ከመሆኑ የተነሳ ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቁ የፍጆታ ዕቃዎችና በአገሪቱ ውስጥ የሚመረቱ ተመሳሳይ ምርቶችን የሚወዳደሩ ዕቃዎች በመግባታቸው(Import)፣ ወደ ውስጥ አጠቃላይ የምርት ክንውን የተዳከመበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህም ማለት በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንውን በማካሄድ ከአንድ ዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመሸጋገርና የስራ መስክ በየደረጃው ከመክፈት ይልቅ፣ መስፋፋት የጀመረው የአገልግሎት መስክና የአገሪቱን የተቆጠበ ሀብት(Scarce resource) የሚጋራ ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀም ነው።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? በኒዎ-ሊበራል ቲዎሪ ላይ የተመሰረተው ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ወደ ተግባር ሲመነዘር ጥቂቱን እያደለበውና አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ ወደ ድህነት እየገፈተረው ነው የመጣው። በአሜሪካና በምዕራቡ ዓለም ቁጥጥር ስር ያሉት የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክም ዋና ሚና በነፃ ገበያ ስም አሳቦ ጥቂቶችን አደልቦ በእነሱ አማካይነት አገሮችን ማፈራረስ ስለሆነ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ቢያንስ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዳይገነባ መንገዱን ማጥበብና አንድ ህዝብ የዝንተ-ዓለሙን እየተደናበረ እንዲኖር ማድረግ ነው። ደሃ አገሮችን በቀላሉ ሊላቀቁ የማይችሉት ወጥመድ ውስጥ በመክተት እዚያ በዚያው እንዲንደፋደፉ በማድረግ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ መሰቃየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ችግሩ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ በመተላለፍ አንድ አገር ህልዋናው እንዳለ እንዲገፈፍ ይደረጋል ። ይህ ዐይነቱ የአገራችንን ሁኔታ ያላካተተና ለሰፊ ገበያና ለውስጥ ከበርቴዎች ነፃ ውድድር የማያመች፣ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የሚደነገገው የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በሁሉም መስክ መዛባትን ነው የፈጠረው። በመጀመሪያው ደረጃ ኢንዱስትሪው በአዲስ መልክ ተዋቅሮና ተስተካክሎ ለሌሎች መሰረት ሊሆኑ በሚችሉ ቲክኖሎጂዎች ላይ ከመረባረብ ይልቅ፣ አሁንም እንደወትሮው የቢራ ፋብሪካ መክፈት፣ የስኳር ተከላ ማስፋፋትና ኢንዱስትሪዎችን መትከል፣ የምግብ ኢንዱስትሪዎች  ማምረቻ ላይ መረባረብ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ የሲሚንቶና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ ነው ርብርቦሽ የተደረገው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የምርት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በመትከል አገሪቱ ከውጭ ጥገኝነት ቀስ በቀ ልትላቀቅ የምትችልበት ሁኔታ በፍጹም ሊዘጋጅ አልቻለም። ከዚህም ባሻገር አሁንም እንደወትሮው „ልማት“ የሚባለው ነገር በአዲስ አበባና በአካባቢው ብቻ የሚካሄድ ስለሆነ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ከተማዎችም ሆነ ትናንሽ ከተሞች መሀከል የልማት ልዩነት መታየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሀብትና የሰው ጉልበት ከሌሎች ክልሎች ወደ አዲስ አበባና አካባቢው በመፍስስ በአጠቃላይ ሲታይ በአገሪቱ ውስጥ የተዛባ ዕድገት እንዲፈጠር ተደርጓል። የውጭውንም ንግድ ስንመለከት የአገሪቱ የውጭ ሚዛን ከዐመት ወደ ዐመት እያሽለቆለቀ የመጣ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያ አሁንም እንደቀድሞው ከቡና ማምረትና ወደ ውጭ መላክ፣ አሁን ደግሞ አበባ አምርቶ ከመላክ የተላቀቀች አገር አይደለችም። ይህ ዐይነቱ በኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ ፖሊሲ አማካይነት በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ድቀትና ውስጣዊ ኃይል አግኝቶ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ በህዝባችን ላይ የደረሰውን የመንፈስ መዳከምና መረበሽ፣ እንዲሁም  የራስ መተማምን እጦት፣ አዳዲስ የፍጆታ አጠቃቀም ያመጣውን በሽታና የባህል ውድቀት፣ በተጨማሪም የቆሻሻ ቦታዎችን መስፋፋትና በአካባቢው ላይ የደረሰውን ጉዳት(Externalities)  በፍጹም አያካትትም። ይህንን አንድ በአንድ እያሉ ከመዋቅር መስተካከያ ፖሊሲ ጋር ማገናኘት ባይቻልም፣ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሃያ ዐመት ጀምሮ የአገራችን ባህልና የማህበራዊ እንዲሁም የአካባቢ ሁኔታ እጅግ በሚዘገንን መልክ እየተበላሸ መምጣቱን መገንዘብ እንችላለን።

ከዚህ አጭር ትንተናዬ በመነሳት ወደ ዶ/ር ዳንኤል አገላለጽ ስመጣ እሱ ማብራራት ያልቻለው በአገራችን ምድር ለተስፋፋው ድህነት ዋናው ምክንያት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ  ፖሊሲ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁንም በማይታይ መልክ ፊይዳላዊ የሚመስሉ ኢንስቲቱሽኖችና የአሰራር ሁኔታዎች ስር በመስደዳቸው ወይም ባለመውደማቸው ያለውን ድህነት ሊያጠናክሩና ህዝባችንን አቅመ-ቢስ ሊያድርጉት በቅተዋል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ድህነት በምናወራበት ጊዜ ከስትራክቸራል ሁኔታ ባሻገር በጊዜው ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጣዊ ይዘትና ዓላማ በደንብ መመርመር አለብን ማለት ነው። እንዲያው የነፃ ገበያ አለመኖርና የመንግስት ጣልቃ ገብነት ናቸው ለድህነቱ ተጠያቂዎች ብለን ብናስቀምጥና ለማስረዳት ብንሞክር የችግሩን ምንጭ ለመረዳት በፍጹም አንችልም። ስለሆነም በአገራችን ውስጥ ስለሰፈነውና ህዝባችንን አቅመ-ቢስ ስላደረገው ድህነት በምናወራበት ጊዜ፣  በውጭ ኃይሎች ግፊትና፣ የውስጥ ኃይሎች ደግሞ በአንድ በኩል ተገደው፣ በሌላ ወገን ደግሞ ካለብዙ ምርምርና ጥናት እንዲሁም ከዕውቀት ማነስ የተነሳ  ተግባራዊ የሚያደርጉትን ፖሊሲዎች ጠጋ ብለን ከሌሎች ቲዎሪዎችና በተግባርም ከተመነዘሩትና ምርቃማ ውጤት ካስመዘገቡ ፖሊሲዎች ጋር ማወዳደር የቻልን እንደሆን የድህነቱና ዋና ምክንያት በደንብ መገንዘብ እንችላለን። ከህብረተሰብ ታሪክ፣ ከባህል፣ ከህሊና አወቃቀር፣ ከመንግስታዊ አወቃቀርና የአገዛዝ ኃይል፣ የንቃተ-ህሊና ጉዳይና የህብረተሰብ ኃላፊነትን የመቀበልና ግንዛቤ የማስገባት ጉዳይ፣ እንዲሁም የውጭ ኃይሎች በአገራችን የመንግስት አወቃቀርና የፖሊሲ አወጣጥና ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት የሚያደርጉትን፣ … ወዘተ. ሳንመረምር ዝም ብለን የምንሰነዝረው አገላለጽ ህዝብን ከማደናበር በስተቀር ለችግራችን መፍትሄ ሊሆን በፍጹም አይችልም።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጓል ወይስ አላደገም ? ዕድገትስ ሲባል ምንድን ነው ?

ዶ/ር ፀሀይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ነው፤ አገሪቱም ትክክለኛውን ፈር ይዛለች ብሎ መጨረሻ ላይ ለማረጋገጥና ለማሳመን የሞከረው አንድ የድሮ አብሮ አደጉን ሰው፣ አሁን በንግድ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚንቀሳቀሰውን እንደምሳሌ በመጥቀስ ነው። እንደነገርን ከሆነ፣ የድሮው ጓደኛው ጋብዞት በመጫወት ላይ እንዳሉ ጋሼ መቼ ነው ወደ አገርህ የምትመለሰው ? ብሎ ይጠይቀዋል። ደ/ር ፀሀይም ከሶስት ዐመት በኋላ እንደሚመለስ ይነግረዋል። አይ ጋሼ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የምትቆይ ከሆነ ስትመለስ ኢትዮጵያን በፍጹም አታውቃትም፤ ቶሎ ብለህ ብትመለስ ይሻላል ብሎ እንደመከረው ቃለ-ምልልሱን ላዳመጠ ሊገነዘበው ይችላል። ከዚህ አባባሉ ስንነሳ ጓደኛው ብቻ በነገረው ሳይሆን፣ እሱም ባየው ሙሉ በሙሉ እንደተደሰተና፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢኮኖሚው ዕድገት የተነሳ በልዩ ዓለም ውስጥ እንደሚኖርና፣ አገሪቱም ልክ እንደሮኬት ተተኩሳ ማንም ሊደርስባት እንደማይችል ነው ሊያሳምነን የሞከረው። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ የምናውቃት ወጣት ጀርመናዊት ድሮ አብራት የተማረችና አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀጥራ የምትሰራ ጓደኛዋን ለመጠየቅ ባለፈው ጥቅምት ወር፣ ከሁለት ወር በፊት ወደ አዲስ አበባ፣ ከዚያም ወደ ደብረሊባኖስ ትሄድላች። ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን ከተመለሰች በኋላ እኛን ለመጠየቅና ስለሁኔታው ልትነግረን ትመጣለች። እኛ ጋ ሁለት ሰዓት በቆየችበት ጊዜ ስለተመለከተችው ሁኔታ ስትነግረን እንባ እየተናነቃት ነበር። እኛ እዚህ በተትረፈረ ዓለም ውስጥ እየኖረን አዲስ አበባ ህዝብ እንዴት በድህነት ሊኖር ይችላል? እንዴትስ የሰው ልጅ በቆሻሻ ሁኔታ ውስጥ ይኖራል? እያለች ነበር እንባ እየተናነቃት የገለጸችልን። ወደ ደብረሊባኖስም ስታመራ የመኪናው ጋጋታና አቅድ ማጣት፣ የተወሰነ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ የሚፈጀውን አሰቃቂ ጉዞ ስታጫውተን፣ ይህ ሁሉ የሚወራለት ዕድገት ፉርሽ መሆኑን መገንዘቡ ቀላል አይደለም። ይሁንና ትላልች ልጂቱ፣ እዚህና እዚያ የሚታዩ አስቀያሚ ጎጆዎች ባይኖሩ ኖሮ ያየችው ቦታ ልክ እንደ ጀርመኑ የባቬሪያ ክፍለ-ሀገር ጋር እንደሚመሳል ነው የተገነዘበችው። የገጠሩን ሁኔታ ካየች በኋላ የተረዳችው ነገር፣ ከህዝቡ ድህነት በስተቀር ይህች አገር ለዕድገት ከፍተኛ ፖቴንሺያል እንዳላት ነው። አዲስ አበባ በቆየችበት ጊዜም መንፈሳቸው የተሰለበ የሚመስል፣ አውሮፓ ውስጥ እንኳ የማይነዳ መኪና ይዘው ሲንደላቀቁ ስታይ በጣም ነው የገረማት። ድህነትና በዘረፋ ኃይል የተገኘ ሀብታምነት እዚያው በዚያው የአገራችን መለዮዎች እንደሆኑ በደንብ ለመገንዘብ በቅታለች። ይህች ወጣት ገና የሃ ስምንት ዐመት ዕድሜ ሲኖራት፣ በትምህርት ደረጃዋም የማስተር ዲግሪ ብቻ ነው የተቀዳጀችው። እንደ ዶ/ር ፀሀይ የፕሮፌሰር ማዕረግነት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። ይሁናን ግን የበሰለ አስተሳሰብና ነገሮችንም በደንብ የመመልከት ኃይል እንዳላት መገንዘቡ ቀላል አይደለም።

የኢኮኖሚስት ምሁሩን ዶ/ር ፀሀይ ብቻ ሳይሆን፣ የወያኔን መንግስትም የሚደግፉ ፈላስፋዎች ነን ባዮች በሙሉ ባለፉት ሃያ ሶስት ዐመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተዓምር እንደተፈጠረ ነው ለማሳመንና፣ የኢኮኖሚው ዕድገትም ምን እንደሚመስል ሊነግሩን የሚሞክሩት። በዚህ የምሁር ስማቸውና አቀራረባቸው የአንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያውያንን ልብና ምንም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ዕውቀት የሌላቸውን ሰዎች ቀልብ ለመሳብና ለማሳመን ሳይሞክሩ አልቀረም። እንዲዚህ ዐይነቱ ምሁር ቴለቪዢን ላይ ወጥቶ „ኢኮኖሚው አድጓል“ ብሎ የምስራች ሲነገርን ግራ ይጋባ የነበረው ወደ ማመን መጠጋቱ አይቀርም። በእርግጥም ላልተማረ ወይም በቂ ኢንፎርሜሽን ለሌለው ሰው የህንፃዎችን ጋጋታ፣ የሆቴል ቤቶችን መሰራትና፣ በመኪና የሚንፈላሰሰውን ሰው ሲያይ በእርግጥም እንደዚህ ዐይነቱ በአንድ አካባቢ አሸብርቆ መታየት የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመስለው ይችላል። በዚያውም ልክ ቆሻሻንና ደሀን ማየት በተለመደበትና ይህም እንደ ባህል ተደርጎ በሚወሰድበት አገር ይህ የተፈጥሮ ህግና ግዴታ መስሎ የሚታየውና በዚያውም የሚኖሩ በአፈጣጠራቸው የተረገሙ ናቸው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይህንን ዐይነቱን የተዛባ አመለካከትና ዕምነት ራሳቸው በአንድ ወቅት ሶሻሊስት ነን ብለው ሲያጨንቁን ከነበሩትና ህዝባችንን እንደቆሻሻ ወደ ማየት ከቀረቡትም አፍ የሰማንበትም ጊዜ ነበር። ሀብት ዘርፎ ማግኘትና በኑሮ መንደላቀቅ በአንድ ወቅት ነቃሁ የሚለውንም አስተሳሰብ እንደሚለውጥ የታዘብንበት ጊዜ አለ። ያም ሆነ ይህ፣ እንደዚህ ዐይነቱን የጥቂቶች የብልግና ዕድገት ከኃይልና ሀብትን ከመመዝበር ጋር የተያያዘ መሆኑን በፍጹም  የማይታየው ጥቂት አይደለም‘። እንደዚህ ዐይነቱ ዕድገት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና በሰፊ የምሁራዊ ኃይል ተደግፎ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ልክ አሸዋ ላይ እንደ ተሰራ ቤት አንድ ጊዜ በሚነሳ አውሎ ነፋስ በቀላሉ ተጠራርጎ እንደሚወሰድ የማይታያቸው ብዙዎች ናቸው።

ይህንን ካልኩኝ ባኋላ በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚን ዕድገት በሚመለከት በሁላችንም ዘንድ መወናበድ እንዳለም መገንዘቡና መረዳቱ ቀላል አይደለም። በኒዎ-ክላሲካልና በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ስለተጻፈውና ስለሚጻፈው የኢኮኖሚ ዕድገት ቲዎሪ በታወቁ ሳይንስቲስቶችና ፈላስፋዎች፣ እንዲሁም ሌላ አመለካከት ባላቸው ኢኮኖሚስቶች ሰፊና አመርቂ ትችት ቢሰጡም አሁንም ቢሆን ከፍተኛ መወናበድ አለ። አብዛኛዎች በጂዲፒ(GDP) የሚገለጸውን፣ ይሁንና ግን ሰለ ዕውነተኛ ዕድገት ብዙም ሊነግረን የማይችለውን የቁጥር ማስረጃ በመውሰድ ነው ኢኮኖሚው በዚህ መጠን አድጓል በማለት ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ አንድ ሰው ዕውነትን ከውሸት ለይቶ ለማወቅ እንዳይችል የሚያደርጉትና ለማሳመን የሚሞክሩት።

በመሰረቱ በአጠቃላይ ስለ አንድ ነገር ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ከጊዜና ከአካባቢ፣ እንዲሁም ከሁኔታ ውጭ ነጥለን ማየት አንችልም። ለምሳሌ አንድን ፍሬ የሚሰጥ አትክልት ብንወሰድ ተክለን ዝም ብለን ፍሬውን ብቻ የምንጠባበቅ ከሆነ አመርቂ ውጤት ልናገኝ እንችልም። ማሰብ የምንችልና አመርቂም ውጤት ለማግኘት ከፈለግን በመጀመሪያ ደረጃ ለመትከል የምንፈልገው አትክልት ቦታው ይስማማው አይስማማው፣ አስፈላጊውን ውሃና ፀሀይ ያግኝ አያግኝ፣ መሬቱ ይስማማው አይስማማው ማጥናት አለብን። ከተተከለም በኋላ በቂ ምርት እስኪሰጠን ድረስ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በኋላ ምርታማነቱ ተከታታይነት እንዲኖረው ከተፈለገ በየጊዜው አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ አለብን። በዚህም መልክ ከአንድ አትክልት በብዛትም ሆነ በጥራት የሚለካና የሚጥም ፍሬ ልናገኝ እንችላለን።

የኢኮኖሚ ዕድገትም እንደዚሁ ጤናማ ጭንቅላት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ተስማሚ አካባቢም ያሰፈልገዋል። የሰው ልጅ ተፈጥሮን ማኒፑሌት ማድረግ እንደሚችል ሁሉ፣ ጭንቅላቱ በደንብ የሚያስብ ከሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትንም እንዲዚሁ ማኒፑሌት ማድረግ ይችላል። ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ሲወራ ከኢንስቲቱሽናዊና ከፖለቲካዊ አወቃቀርና  አመቺ ሁኔታዎች ውጭ በፍጹም ሊታሰብና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም። በተጨማሪም ጤናማ ኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች ሁኔታዎች ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። በታሪክ ውስጥም እንደታየው በመጀመሪያ የባህልና የመንፈስ ተሃድሶ በተካሄደባቸው አገሮች ብቻ ነው ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የቻለውና የሚችለው። ስለሆነም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በአንድ አካባቢ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚያካትትና ጥበባዊ ባህርይ ሊኖረው የሚገባ ነው። በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ምህሮች ዘንድ የተለመደ አመለካከት አለ። ይኸውም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከጊዜና ከቦታ ውጭ የሚካሄድና፣ ፖለቲካና ኢንስቲቱሽኖችም ምንም ዐይነት የሚጫወቱት ሚና እንደሌላቸው ነው። ጥበባዊ ባህርይም ሊይዝ አይችልም። በእነሱ ዕምነት ተጠቃሚው ከፍተኛ ጥቅምን(Maximum Utility) ለማግኝት የሚሯሯጥ ሲሆን፣ ካፒታሊስቱ ደግሞ ከፍተኛ ትርፍ ለማካበት(Maximum Profit) ነው የሚታገለው። ይህም ማለት የአንድ ካፒታሊስት ዋና ዓላማው በመጀመሪያ ደረጃ ትርፍን ለማካበት እንጂ የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አይደለም። ይህ ዐይነቱ  እንደ ርዕየተ-ዓለም የተወሰደው ኢምፔሪሲስታዊ አመለካከት  አስተሳሰባቸውን ማዛባቱ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ብርሃንን እንዳያይ እንቅፋት በመሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ ዘፍቆ አንዲኖር ተገዷል። በእኛ አገርም ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ እንደፈሊጥ በመወሰዱ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው መለኪያው ትርፍ እንጂ የሰውን ልጅ ፍላጎት ማሟላት አይደለም። ስለዚህም የኢኮኖሚ ዋናው ዓላማ  ትርፋማ በሆኑ ነገሮች ላይ መረባረብ እንጂ አገርን በሁሉም አቅጣጫ በተሳካና ተከታታይነት በሚኖረው መልክ እንዲገነባ ማድረግ አይደለም።

ቀደም ብዬ ለማብራራት እንደሞከርኩት ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ከጊዜና ከቦታ፣ እንዲሁም ከፖለቲካና ከኢንስቲቱሽናዊ አመቺ ሁኔታዎች ባሻገር ለሀብት ፈጠራ የሚያግዝ ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ሞዴል(Accumulation Model) መንደፍና መኖር ዋናው መሰረታዊ አስተሳሰብ ነው። በተለይም የፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ከዳበረ ወዲህ በጥንታዊ የኢኮኖሚክስ ምሁራን(Classical Economists) ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ሲወራ እንደ ዋና መሰረታዊ ነገሮች ሆነው የተወሰዱት የሚከተሉት ነገሮች ናቸው። 1ኛ) ሰፋ ያለ ህብረተሰብአዊ የስራ ክፍፍል መኖር። ይህ በራሱ በአንድ በኩል በኢንዱስትሪና በተቀሩት የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል የሚኖረውን የስራ ክፍፍል ሲያካትት፣ በሌላ ወገን ደግሞ በራሱ በኢዱስትሪ ውስጥ የሚኖረውን የስራ ክፍፍል ለዕውነተኛ የሀብት መዳበር ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ይነግሩናል። 2ኛ) የብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ይህንን ወደ ኢንዱስትሪዎች የሚለውጥ የማሺን ኢንዱስትሪ መኖር ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። አንድ አገር የማሺን ኢንዱስትሪና ኢንዱስትሪዎችን ዲዛይን እያደረገ የሚያቀርብ የኢንጂነሪግ ኢንዱስትሪ ከሌላት ሀብት ፈጥራ ሰፋ ወዳለ ገበያ ምስረታ ልታመራ አትችልም። 3ኛ) የተቀላጠፈና በርካሽ ወለድ ብድር ሊያቀርብ የሚችል የባንክ ዘርፍ መኖር ኢንዱስትሪዎችንና የንግድ አንቅስቃሴዋኦችን እንዲዳብሩና እንዲስፋፉ ይረዳል። ይህ ዐይነቱ የተቀላጠፈ የባንክ ዘርፍ በሌለበት አገር ውስጥ ማዕከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ለመዋዕለ-ነዋይ የሚሆናቸውን የገንዘብ ምንጭ ሊያገኙ አይችሉም። 4ኛ) በየደረጃው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔን ህግ ያወቀ መደብ ወይም ሚድል ክላስ መኖር ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። እንደሚታወቀው በካፒታሊስት የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ዕድገት ውስጥ የመጀመሪያው የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ፣ የማስፋፋትና ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀት ያለውና ምርትን በጥራት ሊያመርት የሚችል መዋዕለ-ነዋይ ማካሄድ የዕድገት ዕምብርት ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የካፒታሊዝምን የምርት ክንዋኔ ስንመለከት በ2013ኛዎቹ የሚመመረቱት መኪናዎች ከ1950ዎቹ ጋር ሲወዳደሩ በጥራትም ሆነ በዲዛይን በብዙ እጅ የተሻሉ ናቸው። በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች በአደረጃጀትም ሆነ በቴክኖሎጂዎች እየተሻሻሉ መጥተዋል። ዛሬ ብዙ ኢንዱስትሪዎች በኮምፒዩተር እየተደገፉ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ይህም የሚያመለክተው ባለፈው ሃምሳና ስደሳ ዐመታት ብቻ እንኳ ካፒታሊዝም የቱን ያህል እንደመነጠቀና የሚተከሉትም ቴክኖሎጂዎች የበለጠ እየረቀቁ እንደመጡ ነው። 5ኛ) ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ሲወራ በአንድ አገር ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ደሞዙ በየጊዜው ከምርታማነት ዕድገት ጋር እያደገ መሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ኢንዱስትሪዎች በተከታታይነት ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት ሊያመርቱ የሚችሉት የህዝቡ የመግዛት ኃይል እያደገ የሚሄድ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሰለ ገበያ ኢኮኖሚና ሰፋ ላለ ኢኮኖሚያዊ አንቅስቃሴ ማውራት በፍጹም አይቻልም። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ የሚመረቱት ምርቶች በብዛት እዚያው አገር ውስጥ መሸጥ ስላለባቸው ነው። በሌላ አነጋገር የሰፊው ህዝብ የመግዛት ኃይል እጅግ ደካማ በሆነበት አገር ስለ ገበያ ኢኮኖሚና ስለ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። 6ኛ) ሌላው ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ፣ በአንድ አገር ውስጥ ውድድር የመኖር ጉዳይ ነው። አንደኛው አምራች ከበርቴ ከሌላው በተሻለ ሁኔታ ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ አምርቶ ለገበያ የማያቀርብ ከሆነ ፈጠራ ሊኖር በፍጹም አይችልም።  7ኛ) ፈጠራ(Innovation) ለቴክኖሎጂ ዕድገት ወሳኝና ቁልፍ ቦታን ይይዛል። ለዚህ ደግሞ በመንግስት የሚደገፍና የሚደጎም የቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከላዊ ቦታ መኖር አለባቸው። ዩኒቨርሲትዎችና ኮሌጆችም ለዚህ የተዘጋጁና በራሳቸውም ጥረት እየተመራመሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ መቻል አለባቸው። እነዚህና ሌሎች እዚህ ውስጥ ያልዘረዝርኳቸው ነገሮች በሌሉበት አገር ስለ አኮኖሚ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። ይህም ማለት ምን ማለት ነው? የኢኮኖሚ ዕድገት እንደ አገራችን ወደ ጂዲፒ(GDP) ተቀንሶ በአሃዝ የሚለካ ሳይሆን፣ ብዙ ነገሮችን የሚያካትትና በዐይነትም  ለየት ያለና ሰፋ ባለ መልክ ሊገለጽ የሚችል ነው።

ከዚህ በመነሳት ብዙ የተወደሰለትንና „መንግስታችንም“ የተዝናናበትን የአገራችንን ኢኮኖሚ ዕድገትና ውጤቱን ጠጋ ብለን ለመመልከት እንሞክር። በተለይም ባለፉት አስር ዐመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ11%, በ10%ና አሁን ደግሞ 7% አድጓል እየተባለ ሲነገረን ከርሟል። ይህንን የመንግስትን ዲስኩር የዓለም ኩሙኒቲውም ይጋራዋል። ሁለቱም አልፎ አልፎ በቁጥር ተጋኖ በሚወራው ላይ የሚለያዩ ቢመስሉም፣ በይዘት ግን ይስማማሉ። ይኸውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደ አደገና ኢትዮጵያም  በልዩ ዓለም ውስጥ እንደምትገኝ ነው።  ይሁንና ግን የየሴክተሮችን በኢኮኖሚው ዕድገት ውስጥ ተሳትፎ ስንመለከት የኢንዱስትሪው መስክ አሁንም ቢሆን በአማካይ የጂዲፒ (GDP) አስተዋፅዖው ከ 11% በላይ አይበልጥም። እንደገና የዚህንም መስክ የውስጥ ተቅዋም ጠጋ ብለን በመንመረምርበት ጊዜ አብዛኛዎች ኢንዱስትሪዎች በምግብ ምርት፣ በመጠጥ፣ በቴክስታይልና፣ እጅግ ደካማ በሆኑ የሚታለርጂክ ማኑፋክቱር የሚገለጹ ናቸው። ይህም ማለት በማኑፋክቱር እንቅስቃሴ ውስጥ የማሺንና የኤሊክትሮኒክስ ኢንዱስትሪዎች ይጎድላሉ ማለት ነው። ለዕድገት ከፍተኛውን አስተዋፅዖ አሁንም ቢሆን የእርሻ መስኩ ሲሆን የያዘው፣ በተለይም የአገልግሎት መስኩ ከፍተኛ ድርሻን እየያዘ መጥቷል። ከአገልግሎት መስኩ ደግሞ የሆቴልና የህንፃ ቤት ስራዎች፣ የፋይናንስና የመድህን ኩባንያዎች ቀዳሚ ቦታን እየያዙ መጥተዋል። ይህንን ብዙም የተወደሰለትን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደገና ጠጋ ብለን በምንመለከትበት ጊዜ፣  አብዛኛው ለቤት ስራ የሚያገለግሉና የፊኒሺንግና የመለዋወጫ ዕቃዎችና፣ እንዲሁም የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ከወጭ የሚመጡ ናቸው። እነዚህ ውጭ ተመርተው ወደ አገር ቤት ውስጥ የሚገቡትን ማሺኖችና የመለዋወጫ ዕቃዎች አገሪቱ ውስጥ ከተመረተው ጠቅላላ ምርት ነጥለን ብናወጣ ኢኮኖሚው እንደሚባለውና መንግስትም እንደሚደሰኩረው እንዳላደገ መገንዘብ እንችላለን። በኢኮኖሚ ስሌት አንድ አገር ውስጥ በራስ ጥረት ተጨማሪ ምርት ከተመረተና ካለፈው ዐመት ጋር ሲወዳደር የበለጠ ከሆነ ኢኮኖሚው በዚህ መጠን አድጓል ማለት ይቻላል። ይህም ሆኖ ይህ በራሱ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በቂ ስዕል ሊሰጠን በፍጹም አይችልም። ከላይ በሰፊው ለማብራራት እንደሞከርኩት የዘረዘርኳቸው ነገሮች የተካተቱ እንደሆነ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ይህን ያህል በቁጥርም ሆነ በይዘት አድጓል ማለት ይቻላል።

በሌላ ወግን ዶ/ፀሀይ፣ ወያኔንም ሆነ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የሚባለው፣ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያወሩትን እንቀበል ብንል እንኳ ለምን አገሪቱ አሁንም በድህነት ዓለም ውስጥ ዘፍቃ ትገኛለች? ለሚለው ጥያቄያችን መልስ ልናገኝ በፍጹም አንችልም። በዶ/ር ፀሀይ አሰላል መሰረት ዛሬ ኢኮኖሚው ማደጉን ማረጋገጥ የሚቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከሰላሳ ዐመት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲወዳደር ከ$ 120 ወደ $ 300 እንደጨመረ ነው። በሌላ ወገን ግን የነፍስ ወከፍ ገቢ ማደግ ብዙም የሚነግረን የለም። መነሳት ያለበት 1ኛ) ሁሉም ሰው ይህንን ያህል ገቢ በዐመት ያገኛል ወይ ? መልሱ ባጭሩ አያገኝም የሚል ነው። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ የሚመረት ዐመታዊ ጠቅላላ ምርት በገንዘብ ተሰልቶ ለኗሪው ህዝብ በሚካፈልበት ጊዜ እያንዳንዱ ግለሰብ ይህንን ያህል ይደርሰዋል ብሎ መናገር ትልቅ ስህተት ነው። 2ኛ) በዚህ የነፍስ ወከፍ ገቢ እያንዳንዱ ዜጋ ምን ምን ነገሮችን ገዝቶ ሊጠቀም ይችላል ? ቤትስ መከራየት ይችላል ወይ? ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ከገዛና የቤት ኪራይም ከከፈለ በኋላ፣ የተወሰነውን በቁጠባ መልክ ሊያስቀመጥ ይችላል ወይ? ለሚለው ጥያቄያችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ማደጉ ይህንን ያህልም የሚነግረነ ነገር የለም።  3ኛ) የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠረውን የሀብት መሸጋሸግ ሊነግረን አይችልም።  ለምሳሌ ባለፉት አስርና አስራአምስት ዐመታት በአገራችን በጥቂት ሰዎች እጅ እየተከማቸ የመጠውን ሀብት ስንመለከት ጂኒ ከኦፊሴንቱ 0.47 እንደሆነ እንመለከታለን። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ የገቢው ሁኔታ ከአልቦ እየራቀ ወደ አንድ በተጠጋ ቁጥር አብዛኛውን ገቢ የሚያገኙ ሰዎች በጣም ጥቂት እንደሆኑ ነው። 4ኛ) ከዛሬ ሰላሳ ዐመት በፊት የነበረው የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ$120 ወደ $300 ማደጉ በሰላሳ ዐመታት ጊዜ ውስጥ የዶላርን የመግዛት ኃይል መዳከም የሚያካትት አይደለም። በሌላ አነጋገር ከሰላሳ ዐመት በፊት የነበረው አንድ ዶላር የመግዛት ኃይሉ ከዛሬው ጋር ሲወዳደር እጅግ ከፍ ያለ ነው። ለምሳሌ ከሰላሳ ዐመት በፊት የነበረው $120 የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2014 ዓ.ም ጋር ሲወዳደር $286 ያህል የመግዛት ኃይል አለው ማለት ነው። ይህንን ሁሉ ትተን  የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው ዓላማው ድህነትን ማስወገድ ከሆነ አገራችን አሁንም ቢሆን ለምን በአስከፊ ሁኔታ በድህነት ዓለም ውስጥ እንድትገኝ ተገደደች? ለሚለው አንገብጋቢው ጥያቄያችን ዶ/ር ፀሀይ አጥጋቢ መልስ ሊሰጠን በፍጹም አይችልም። ያም ሆነ ይህ የኢኮኖሚው ዕድገት፣ ዕድገት እንደማይባል፣ ድህነትን ከመቅረፍ ይልቅ ድህነትን እንዳባባሰና፣፣ ህዝባችንንም የባሰ ጥገኛና አቅመ-ቢስ እንዳደረገው የሚቀጥሉትን አሃዝ መመልከቱ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማደግና አለማደግ የበለጠ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከኒጄር ቀጥሎ ሁለተኛዋ የመጨረሻ ደሃ አገር ነች። 25 ሚሊዮን ህዝብ ወይም 27 በመቶ የሚጠጋ ህዝባችን አስከፊ በሆነ የድህነት ዓለም ውስጥ የሚገኝ ነው። አሁንም ቢሆን ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከውጭ በሚመጣ የዕርዳታ እህል የሚመካ ነው። ይህም ማለት አገሪቱ በራሷ በበቂው አምርታ ህዝቧን ልትመገብ አትችልም ማለት ነው። ይሁንና እዚያው በዚያው ደግሞ መንግስት ማንም ሳያዘው በገዛ ፈቃዱ እየተነሳ የአገሪቱን ምርታማ መሬቶች እያከራየና ገበሬውን እያፈናቀለ፣ መሬቱ ላይ የሚመረተው ምርት ወደ ውጭ እንዲጓዝ ያደርጋል። ዶ/ር ፀሀይ ይህንን የመሰለውን የመሬት መቀራመትና ገበሬውን ማፈናቀል እንደ መዋዕለ-ነዋይ ይመለከተዋል። ይህ ዐይነቱ መሬትን መቀራመትና ገበሬውን አፈናቅሎ አርሶ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ በኢኮኖሚውና በአካባቢው ኗሪ ህዝብ የማህበራዊ ህይወት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ውጤት ዶ/ር ፀሀይ በደንብ የተገነዘበ አይመስልም። 1ኛ) ኢንቬስተሮች የሚባሉት ለአካባቢው ዕድገት፣ ለህዝቡ የኑር መሻሻልና ባህላዊ ለውጥ፣ እንዲሁም ህበረተሰብአዊ ትስስርና የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። በአንፃሩ እስከዛሬ ድረስ ከትውልድ ወደ ትውልድ የዘለቁትን እሴቶችና የአኗኗር ስልቶች በማፈራረስ ገበሬውንም ወደ ተራ ገባርነት እንደለወጡት እንመለከታለን። 2ኛ) የውጭ ኢንቨስተሮች ለጠቅላላው ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። እህሉ ወደ ውጭ በሚላክበት ጊዜ ገንዘቡ የውጭ አገር ባንክ ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረገል። ገንዘቡ ወደ አገራችን መጥቶ ለመዋዕለ-ነዋይ እንዲውል አይደረግም። መንግስትም በቀረጥ አማካይነት የሚያገኘው ይህ ነው አይባልም። 3ኛ) ይህ ዐይነቱ የመሬት ቅርሚት አገራችንን ቀስ በቀስ ወደ የእጅ አዙር ቅኝ-ተገዢነት እየለወጣት በመምጣት ላይ ነው። አገዛዙ በዚህ መልክ የአገራችንን ፍሬያማ መሬት ለውጭ ከበርቴዎች እየሸበሸበ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሰብአዊ ዕርዳታ(Humanitarian Aid) በሚል ሰበብ በየዐመቱ ከ$3 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ  ዶላር  ያገኛል። ይህ ርዳታ የመንግስቱን ዐመታዊ ባጀት 50-60 % ይይዛል። ከዚህ ባሻገር አገራችን በዩናይትድ ኔሽንስ የዴቬሎፕሜንት ፕሮግራም በተጠናቀረው ጥናት መሰረት በዓለም ደረጃ በሰብአዊ የዕድገት መለኪያ መሰረት(Human Development Index) በ2013 ዓ.ም ከ187 አገሮች ውስጥ 173ኛውን ይዛለች። በኦክስፎርድ የድህነትና የሰው ልጅ ዕድገት ተነሳሽነት በተጠናቀረው የጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በተወሳሰበ የድህነት ሁኔታ(Multidimensional poverty) የምትጠቃ አገር ነች። ይህ ዐይነቱ የተወሳሰበ የድህነት ጥቃት በአስፈላጊው የምግብ እጥረት፡ በህክምና ችግር፣ በንጹህ ውሃ ማጣት፣ በተስማሚ ቤት አለማግኘት፣ በትምህርት ቤት ችግር፣ በመቀቀያ እጥረትና እነዚህን በመሳሰሉት የሚገለጽ የድህነት ሁኔታ ነው። ይሁንና ይህ አሁን በዩናይትድ ኔሽንስ ዴቬሎፕሜንት ፕሮግራም የተወሰደው የድህነት መለኪያ ዘዴ ለዚህ የዳረገንን ምክንያት በዝርዝር አያስረዳም። እንዲያው ብቻ፣ የድህነቱ ጥልቀትና ስፋት በዚህ መልክ ይገለጻል ከማለት በስተቀር ወደ ውስጥ በመግባት የድህነቱን ዋና ምክንያት ሊጠቁመን የሚችል ጥናት አይደለም። የችግሩን ምክንያት እስካላወቅን ድረስ ደግሞ በሎጋሪዝም የማቲማቲካል ሞዴል ተጠናቅሮ የቀረበው ማስረጃ ችግሩን ከስር እንድንነቅል የሚያስችለንን መሳሪያ እንድንፈልግ የሚረዳን አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ የዩናይትድ ኔሽንስ ዴቬሎፕሜንት ፕሮግራም በሶስተኛው ዓለም ውስጥ ዕውነተኛ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ እንዳይጠፋና አገሮች ዕውነተኛ ብሄራዊ ነፃነታቸውን እንዳይቀዳጁ ሴራ ከሚሸርቡት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ በውስጡ  ጆን ፐርኪንስ የሚባለው የሲ አይ ኤ ሰው የነበረው እንደሚለው የኢኮኖሚ ዕድገት አሳሳቾች ወይም ኢኮኖሚክ ሂት ሜን ብሎ የሚጠራቸው የተሰገሰጉበት ድርጅት ለመሆኑ በግልጽ የታወቀ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የችግሩን ምንጭ ከሳይንስ አንፃር ሊነግረንና መፍትሄውንም ሊጠቁመን አይችልም ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ በዚሁ የተወሳሰበ የድህነት ጥልቀት መለኪያ መሰረት 87.3% የሚሆነው ህዝባችን በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኝ ነው። ከዚህም በላይ 6.8% የሚሆነው ደግሞ ለከፍተኛና ለባሰ ድህነት የተጋለጠ ሲሆን፣ ከሁሉም ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ክንዋኔዎች የተገለለ ነው። በዚህም መሰረት አገሪቱ በገንዘብ ሲተመን ወደ $4.7 ቢሊዮን የሚጠጋ የሰው ኃይል ታጣለች። ገፋ ብለን ስንሄድ ደግሞ አንድ ግለሰብ በየቀኑ በነፍስ ወክፍ የሚያገኘው ከአንድ የአሜሪካ ዶላር በፍጹም አይበልጥም። ይህንን ያህል ሳያገኝ የሚውል በብዙ መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ እንዳለ መገመቱ ቀላል አይደለም። ከዚህም በላይ ከአምስት ህፃናት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ የማሰብ ኃይላቸው ደካማ ነው። በንጽህና ጉድለት የተነሳ ከስምንት ህጻናት ውስጥ አንድ ህጻን አምስት ዐመት ከመሙላቱ በፊት ይሞታል። 20% የሚሆነው የህፃናት ሞት ዋናው ምክንያት አስፈላጊውን ለሰውነት መገንቢያ የሚጠቅመውን ምግብ ካለማግኝት የተነሳ ነው። ወደ አጠቃላዩ ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ፣ 54% የሚሆነው ህዝባችን ንጹህ ውሃ የማግኘት ዕድል የለውም። 87.6% የሚሆነው ደግሞ መጸዳጃ የለውም። 85.7% የሚሆነው ህዝባችን የመብራት ኃይል የማግኘት ዕድል የለውም። 89.6% የሚሆነው ህዝብ ደግሞ ለመቀቀል የሚያገለግል ነዳጅም ሆነ እንጨት የማግኘት ችግር አለበት። 80% የሚሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ደግሞ በቆሻሻ ቦታዎች ነው የሚኖረው።  ይህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታ የሚታየውና ህዝባችንም የሚሰቃየው ኢኮኖሚው እንደ ሮኬት ተተኩሷል በሚባልበት አገር ውስጥ ነው። ውድ ወንድማችን ዶ/ር ፀሀይን ልጠይቀውና፣ እንደዚህ ዐይነት ስቃይ የሚያስከትል፣ ድህነትን የሚፈለፍልና ለለማኝነት የሚዳርግ ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት ነው? ኢኮኖሚ ሲባልስ ድህነትን መፈልፈያ ወይስ ድህነትን አስውግዶ አገርን መገንቢያ ዘዴ ? መልሱን ለአንባቢው እንድተመልስ በክብር እጠይቅሃለሁ።

ይህ በዚህ ዐይነት የሚገለጸውና በዐይናችን የምናየውና የዓለም ማህበረ-ሰብ የሚሳለቅብን ድህነት ዋናው ምክንያት ምንድነው ? ይህ ዐይነቱ ጥያቄ እስካሁን ድረስ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ምሁራን ያልተነሳና ለውይይትም ያልቀረበ ጉዳይ ነው። እኔ እስከማውቅው ድረስና የአውሮፓውን የህብረተሰብና የኢኮኖሚክስ ታሪክ እንደተከታተልኩት ከሆነ፣ ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የፈለቁ ምሁራን በየኤፖኩ በየአገሮቻቸው ውስጥ የነበረውን ችግር ምክንያት በፍልስፍናና በሳይንስ መነፅር ሳይመረምሩ ወደ አንዳች መፍትሄ ያመሩበት ጊዜ አልነበረም። በየአገሮቻቸው የነበረውን የጠለቀ ችግር አድበስብሰው ያለፉበት ጊዜ በታሪክ ውስጥ አይታይም። አመለካከታቸውም ሁለንታዊ በመሆኑ በጊዜው የተሻለ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያገዱትን ነገሮች ሁሉ በተለይም በፍልስፍና መነፅር መመርመርና መፍትሄ መስጠት ብቻ ሳይሆን በግልጽ ወደ ውጭ አውጥቶ መናገርና መከራክር የአውሮፓ ምሁራን ባህል ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህም በመነሳት ሳይፈሩ ሳይቸሩ ወደፊት ወጥተው በመከራከር በጊዜው የነበረው ኋላ-ቀር አመለካከት እንዲወገድና ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ እንዲዳብርና፣ ይህም በመንግስታት ላይ ተጽዕኖን እንዲያሳድር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህ በራሱ ለፖለቲካና ለኢንስቲቱሽን ሪፍሮሞች መንገድ በመክፈት ኋላ-ቀር በሆኑና ሳይንስንና ቴክኖሎጂን በሚፈልጉና ለዚህም በሚታገሉ መሀከል የተጧጣፈ ትግል ለማካሄድ ችለዋል።

ወደ አገራችን ስንመጣ ግን በየጊዜው ስልጣን ላይ የወጡ ኃይሎች በዚህ ዐይነቱ የምሁር እንቅስቃሴ ትግልና የመንፈስ ተሃድሶ ሂደት ውስጥ ስላላፉና ከውጭም ትግል ስለማይካሄድ አዲስ ኃይል ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሰበጣጠር የእኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ የባሰ ድህነትንና መዘበራረቅን ያስከትላል። እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ የውጭ ኃይሎች ትዕዛዝ አስፈጻሚ በመሆን የአገራችን ድህነት እንዲባባስና ህዝባችንም ወደ ለማኝነት እንዲገፈተር ያደርጋል። የዛሬውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመረምር ዋናው ችግር ከዚህ የመንፈስ ተሃድሶ ካለመኖር ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። ዛሬ ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በዕልክ የሚወስደው ፖሊሲ ከዚህ የመንፈስ ተሃድሶ ዕጦት የመነጨ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንዳለ በውጭ ኃይሎች በርቀት መቆጣጠሪያ ትዕዛዝ እየተቀበለ ወደ ተራ አሽከርነት የተለወጠ የሚመስል አገዛዝ ነው ስልጣንን የጨበጠ። በመሆኑም፣ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን ኋላ-ቀር ኢንስቲቱሽኖች ለሱ መገልገያ በማድረግና ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣ አግዷል። በዚህ ብቻ ሳይወሰን፣ የፖለቲካና የሚሊታሪ የበላይነትን ተቀዳጅቻለሁ በማለት ሌሎች ኃይሎች በኢኮኖሚው ውስጥ ገብተው እንዳይሳተፉና የየበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዳያደርጉ መንገዱን ሁሉ ዘግቷል።  በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን ደግሞ በሆነ  ባለሆነ መንገድ በማሳበብ ገበያውን ለቀው እንዲወጡ በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመጣ ሰፊ መሰናክል ሆኗል። በዚህ ብቻ ሳይወሰን በየክልሉ ህዝቡ አብሮ በጋራ እንዳይኖርና እንዳይሰራ የከፈፍለህ ግዛ ፖሊሲ በማካሄድ መረጋጋት እንዳይኖር አደገኛ ጨዋታ ይጫወታል። ከዚህም በላይ ለውጭ የስለላ ድርጅቶች በሩን በመክፈት በየገጠሩ በሃይማኖት ስም አሳበው በመግባትና በመሰማራት በተለይም የደቡቡ ህዝብ በአማራው ብሄረሰብ ላይ እንዲነሳና የርስ በርስ ጦርነት እንዲካሄድ የማይሸርቡት ተንኮል ይህ ነው አይባልም። በዚህ ዐይነት እጅግ በተበላሸና በተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። አንድ ቦታ ላይ እንዳልኩት፣ አንድ አትክልት ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ አካባቢው ብቻ ሳይሆን መስማማት ያለበት፣ በየጊዜው እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ለጤናማ ብሄረ-አቀፍ ኢኮኖሚ ዕድገትም አመቺ የሆነ  የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የባህላዊ  ሁኔታዎች መፈጠርና መኖር እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ከዚህም ባሻገር የውጭ ኃይሎች ባገራችን ገበተው እንደፈለጉ የሚፈተፍቱት ጫወታ መቆም አለበት። በህዝብ ላይ አመኔታ ያለው መንግስት እስከሌለ ድረስና፣ ብሄራዊ ነፃነታችን እስከተገፈፈ ድረስ፣ እንዲሁም ደግሞ አንዳንድ መንግስታት የተሰጣቸውን ሰፊ የኤምባሲ ግቢ ተገን አድርገው የአገርን ደህንነት የሚጎዳ ስራ እስከሰሩ ድረስ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትና ስለ ህብረተሰብ ግንባታ በፍጹም ማውራት አይቻልም።  ስለዚህም ለዕውነተኛ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚደረገው ትግል ከፖለቲካ ነፃነትና የብሄራዊ ነፃነትን መልሶ ከመቀዳጀት ውጭ ተነጥሎ በፍጹም ሊታይ አይችልም። በመሆኑም ምሁር የሚባለው ኃይል የህብረተሰባችንን ችግር ዋናው ምክንያት ወደ ውጭ አውጥቶ መወያየትና መከራከር እስካልቻለ ድረስና፣ ትግልም እስካላደረገ ድረስ በአገራችን ምድር በፍጹም ለውጥ ሊመጣ አይችልም። በኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲና በውጭ ኃይሎች ድጋፍም አንድ የተከበረች አገር መገንባት እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር የዛሬው አገዛዝ ከስልጣን ቢወገድም ህዝባችን የሚመኘውን ዕውነተኛ ዕድገትና ብሄራዊ ነፃነት ለመቀዳጀት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከበፊቱ እንደሚደቀኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ በራሳቸው ዓለም ውስጥ በሚኖሩትና በሰው ልጅ በሚቀልዱት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶችና ተከታዮቻቸው ካልሆኑ  በስተቀር፣ ለተገለጸላቸው ምሁራንና ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግልጽ ነው። እነዚህ ምሁራን ነን ባዮች የፈለጉትን ያህል ስለኢኮኖሚ ዕድገት ቢነግሩንም በምድር ላይ ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ሊያመልጡና ሊያሳስቱን በፍጹም አይችሉም።  በሌላ ወገን ግን መታወቅ ያለበት አንድ ጉዳይ አለ። በህብረተሰብ የዕድገትና አገር የመገንባት ታሪክ ውስጥ ህዝባዊና ህብረተሰባዊ ዕድገትን አምርረው የሚጠሉ እንዳሉ መታወቅ አለበት። ለሰው ልጅ ደህንነትና የኢኮኖሚ እኩልነት ብልጽግና ትግል ከተጀመረ ወደ 2 500 ዐመት ሊሆነው ነው። አንድን ህዝብ ማሳሳትና ደሃ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን፣ በእነሶክራተስና ፕላቶ ዘመንም ለጥቂት የኦሊጋርኪ መደብ የቆሙ ኃይሎች የሰፊውን ህዝብ ስልጣኔና በዺሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ በመሳተፍ የዕድሉ ወሳኝ እንዳይሆን የሚሆነውን የማይሆነውን የሚያወሩና ወጣቱን የሚያሳስቱና ቀናውንም የስልጣኔ አጥብቀው የሚጠሉ እንደነበሩ መታወቅ አለበት። ከ17ኛው ዓ.ም ጀምሮ የሊበራሊዝም ርዕዮተ-ዓለም ሲስፋፋ ዋና ዓላማውም  በጊዜው ብቅ ያለውን የኃይል አሰላለፍ ርዕዮተ-ዓለማዊ ሌጂቲመሲ ለመስጠትና፣ የሰው ልጅም ዕድል በዚህ ክልል ውስጥ ብቻ ነው የሚወሰነው፣ ከዚህ ሌላ አማራጭ የህብረተሰብ ስርዓት ሊኖር አይችልም በማለት ነበር የሚሰበከው።  ካፒታሊዝም የበላይነትን እየተቀዳጀ ሲመጣ ርዕዮተ-ዓለማዊ ትግሉ ውስብስብ እየሆነ በመምጣት የሰው ልጅም አስተሳሰበ የበለጠ በክስተታዊ ግን ደግሞ ጊዜያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ውስብስብ የሆነ የፍጆታ አጠቃቀም ሃይማኖትን በመተካት የሰው ልጅ ዕድልም ገንዘብ በማግኘትና ተራ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ብቻ እንዲመሰረት ተደረገ። የሰውም የርስ በርስ ግኑኝነት በገንዘብ የሚገለጽ በመሆን፣ ገንዘብ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትን  ደንጋጊ ኃይል ሆነ። በተለይም ባለንበት ዘመን፣ ብልጭልጭ ቴክኖሎጂዎች የሰውን ልጅ አስተሳሰብ በመቅረጽና አትኩሮውንም ውስን እንዲሆን በማድረግ ውሸትን ከዕውነት ሊለይ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ቴኮኖሎጂያዊ ዕድገት ጥሩ የሆነውን ያህል ወደ አገዛዝና የሰውን ልጅ እንቅስቃሴና ድርጊት መቆጣጠሪያ መሳሪያ በመለወጥ የሰው ልጅ አስተሳሰብ ጥልቀት እንዳይኖረው ለማድረግ ተችሏል።  ይህ ሁኔታ  ምሁራን ነን ለሚሉና ለተወሰነ የህብረተሰብ ጥቅም ለቆሙ ለማወናበድ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። በመሆኑም  በተለይም የኢኮኖሚ ኤክስፐርት ነን እያሉ የሚሆነውን የማይሆነውን በማውራትና  ለማንኛውም ተራ ሰው የማይገቡ የተወሰኑ ቃላት በመወርወር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን ሀዝብ ማወናበድ ችለዋል። እንደነዚህ ዐይነት ኤክስፐርት ነን ባዮች እንደ አምላክ እየታዩና እየተፈሩ ለድህነት መፈልፈል ዋናው ምክንያት እየሆኑ ነው። የጊዜውም አንገብጋቢ ጥያቄ በምን መልክና እንዴት ይህንን የተወሳሰበ ሁኔታ በቀላል ቋንቋ ለሰፊው ህዝብ ማስረዳት ይቻላል?  የሚለው ጥያቄ ነው ሀቀኛ ምሁራንን የሚያስጨንቃቸው። በሌላ ወገን ግን  ወደ ኃያልነት የተለወጡና ቴክኖሎጂን የተቀዳጁ አገሮችን ታሪክ ስንመለከት ለብሄራዊ ነፃነት የሚደረገው ትግል በዩልኝታ የሚካሄድ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። አንዳንድ ጊዜ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ጉልበት ወይም ኃይል ለህብረተሰብ ዕድገት ወሳኝ ሚናን የሚጫወትበት ጊዜ እንዳለ ከብዙ አገሮች ታሪክ የምንማረው ሀቅ ነው። በተለይም በዚህም በዚያም ብለው ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ዕድገትና ስልጣኔ እንዳይመጣ የሚታገሉ ኃይሎች ስላሉ፣ እነዚህን የመቆጣጠሩና በመንግስት መኪና ውስጥ ተሰግስገው እንቅፋት እንዳይሆኑ ቆራጥ ትግል ማካሄድ እንደሚያስፈልግ መታወቅ አለበት። ማንም በምሁር ስም እየተነሳ የሚያወናብድበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ግልጽ ትግል ማካሄድ ለአንድ ህብረተሰብ ጤናማ ስርዓትና ለህዝብ ተቻችሎ መኖር አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር መታወቅ አለበት።

           የብድርና የውጭ መዋዕለ-ነዋይ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ሚና !

ሰሞኑን አነጋጋሪው ጥያቄ ደግሞ የወያኔ አገዛዝ ከውጭ መንግስታት የተበደረውና አሁን ደግሞ ከካፒታል ገበያ ላይ የውጭ ከረንሲ ለመቃረም ሲል ያወጣው የመንግስት መረጋገጫ ወረቀት(State Bond) ነው። በእኛ በኢትዮጵያኖች መሀከል ያለው አስቸጋሪ ነገር አንድ ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ እሱን ከሌሎች ነገሮች ነጥሎ  በማውጣት መረባረብ ነው።

ለማንኛውም ማንም ጤናማ ሰው መጠየቅ ያለበት ቀላል ጥያቄ አለ። ይኸውም የአንድ አገር ኢኮኖሚ እያደገ ከሄደ፣ ያውም 11% ለምን በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ብድር አስፈለገ?  ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። የአገራችንን በዕዳ መተብተብ- ምናልባት $14 ቢሊዮን ምንም ላይመስለን ይችል ይሆናል- መረዳት የምንችለው አገዛዙ ባለፉት 23 ዐመታት ተግባራዊ ያደረገውን አገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ውጤቱን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ በዕዳ መተብተብ በአገራችን ብቻ የተከሰተ ሳይሆን፣ የመዋቅር መስተካከያ ወይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያካሄዱ አገሮች፣ እንደ ጋናና ናይጀሪያ በሰማኒያኛው ዐመታት፣ እነ አርጀንቲናና ብራዚልም እንዲሁም ሜክሲኮ የመሳሰሉ አገሮች ያለፉበትና መቀመቅ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ዐይነት ነው። በሌላ አነጋገር፣ በዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ተጠናቅሮ የወጣው ፖሊሲ እነዚህን አገሮች ወደ ውስጥ ያተኮረ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ  የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዳያካሂዱ በማገዱና ፖሊሲውም የማምረት ኃያላቸውን በማዳከሙ የግዴታ ወደ ብድርና ዕዳ ውስጥ እንዲወድቁ አስገድዷቸዋል። የእነዚህን አገሮችም አጠቃላይ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ሁኔታ ስንመለከትና ስንመረምር፣ በመዋቅር መስተካከያ ወይም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት በየአገሮች ውስጥ የውስጡን ገበያ የሚያዳክምና ከውጭ የሚመጡ የቅንጦት ዕቃዎችን የሚያሳድግ ሁኔታ እንደተፈጠረ እንመለከታልን። በሌላ አነጋገር፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እየተደገፉ ምርትን በጥራትም ሆነ በብዛት አሳድጎ የውስጥ ገበያን ከማስፋፋት ይልቅ፣፣ ገበያው ለውጭ ዕቃ ክፍት እንዲሆን በመደረጉና፣ ከየአገሩ የኢኮኖሚ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ሊጣጣም የማይችል አዲስ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀም በመለመዱ የንግድ ሚዛናቸው እንዲዛባና ብድር ወጥመድ ውስጥ በመግባት የወለድ ወለድ ከፋይ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ፣ 1ኛ) ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ገበያ መገንባት አልተቻለም፤  2ኛ) የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት አገዛዙ አሁንም የሚመካው በእርሻ ውጤት ላይ፣ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጨአት፣ እጣንና ስኳር፣ …ወዘተ. የመሳሰሉት ላይ ነው። ይህ ዐይነቱ የአወቃቀር ድክመትና፣ ከዚህ ዐይነት የኤክሶፖርት ኢኮኖሚ ለመላቀቅ አለመቻል  አገዛዙ ዐይኑን ወደ ውጭ እንዲመለከት አስገድዶታል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከህዝቡ ፍላጎት ጋርና ከአገሪቱ አቅም ጋር የማይመጣጠን የአጭርና የረዠም ጊዜ ህይወት ያላቸው የፍጆታ ዕቃዎች በማስገባት የውጭው የንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ እንዲዛባ ለማድረግ በቅቷል። የውጭው የንግድ ሚዛን መዛባት እንደየስሌቱ ከ$3- $7 ቢሊዮን እንደደረሰ ይታወቃል። ከዚህም በላይ ተግባራዊ የሚሆኑት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ብዙ የውጭ ከረንሲ ስለሚጠይቁ ዛሬ በዕዳ የመተብተብን ሁኔታ ሊፈጥር ችሏል። ባጭሩ ነገሩን ይበልጥ ለመረዳት በደንብ ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ እስካልተካሄደ ድረስ ዕዳና ጥገኝነት ለረዥም ጊዜ የአገራችን መለዮዎች ሆነው ይቀራሉ። በሌላ ወገን እ.አ ከ200-2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ከአገሪቱ ወደ ውጭ በግምት $24 ቢሊዮን ካፒታል እንደሸሸና የውጭ አገር ባንኮችን እንደሚያደልብ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ ወርቅና ሌሎች የማዕድን ሀብቶች በግልጽና በድብቅ እየወጡ ከሺያጭ የሚገኘው ዶላር እዚያው የውጭ አገር ባንኮች ውስጥ በቀመጥ እያደለባቸው ነው። አገዛዙ ይህንን ወደ ውጭ የሸሸ ገንዘብ ነው በተዘዋዋሪ በመበደር የወለድ ወለድ ከፋይ የሚሆነውና ለአገራችን ጠንቅ ጥሎ ለመሄድ የተዘጋጀው። የካፒታል ሽሽት ባይኖርና ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገቡትም ዕቃዎች ከአገራችን ኢኮኖሚና ህዝብ ፍላጎት ጋር እየተነፃፀሩ ቢገቡ ኖሮ አገዛዙን እንዲበደር  የሚያስገድደው አንዳችም ነገር አልነበረም። በተጨማሪም የኢኮኖሚው ፖሊሲ በአገሪቱ ሀብት ላይ ያተኮረና ሰፊውን ህዝብ በግንባታ ክንዋኔ ውስጥ ሊያካትት የሚችል ሆኖ የታቀደ ቢሆን ኖር እንደዚህ ዐይነቱ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ ባልገባን ነበር።

የዚህ አሉታዊ ውጤት ምንድነው ? እንደሚታወቀው አንድ ግለሰብም ሆነ አንድ መንግስት ብድር ሲበደር የግዴታ በስምምነቱ መሰረት ወለድ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ዋናውን ብድርና ወለዱን ጠቅላላው ዕዳ እስካለቀበት ጊዜ መክፈል አለበት። በየጊዜው ወለዱንና ዕዳውን መክፈል እሳካልቻለ ድረስ ደግሞ የግዴታ  የወለድ ወለድ(Compound Interest) በመክፈል የዕዳው መጠን እየተቆለለ ይሄዳል። ለምሳሌ የአርጀንቲናን ሁኔታ ብንመለከት ዋናው የተበደረችውን ካፒታል ሙሉ በሙሉ መልሳ ብትከፍልም፣ የወለድ ወለዱ እየተከማቸ በመምጣቱ ከሃያና ከሰላሳ ዐመታት በኋላ አሁንም ቢሆን ከዕዳው ባለመላቀቅ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብታ ትሰቃያለች። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጥተኛ ብድር እንበለው ወይም በቦንድ መልክ መጣ እንበለው አንድ አገር ዕዳውን መክፈል የማትችል ከሆነ በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድረጅት አማካይነት የአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ((Austerity Program) እንድትከተል ትገደዳለች። ልክ አርጀንቲና ውስጥ በዘጠናኛው ዐመት እንደተመለከትነውና፣ አሁን ደግሞ ግሪክ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንደሚያረጋግጥልን በአውስተሪቲ ወይም በአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ የአንድ አገር ኢኮኖሚ እንዲፈራስና መንግስታትም የሚመኩበት ጥቂት የህዝብ ሀብት ወደ ግል እንዲዛወር በማድረግ ዕዳውን እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። የነፃ መንግስታት ብድር( Sovereign Debt) የሚባለውና ብዙም መዝናናት የሚታይበት የመጨረሻ መጨረሻ ነፃነታቸውን እንዲያጡና ህዝቦቻቸውን እንዲያደኸዩ ይገደዳሉ ማለት ነው። ስለሆነም የአገራችን አገዛዝ የተበደረውን ብድርና አሁንም ደግሞ የበተነውን ቦንድ በዚህ መልክ ነው መረዳት የሚቻለው። በዚህ ዐይነት አገዛዝ ብድሩ ምርታማ ነገር ላይ ውሎ፣ ኢኮኖሚውን በማሳደግ የመጨረሻ መጨረሻ ትርፍ በማትረፍ ዕዳውን መክፈል ይቻላል የሚለው እጀግ አደገኛ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋውን የካፒታሊስት ኢኮኖሚና አገሮችን በሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ የሚጠቀምበትን ልዩ ልዩ ዘዴዎች አለመረዳት ነው።

የመንግስትን ዕዳና ብድር እንዲሁም የውጭ ከበርቴዎችን-ባንኮች- አስመልክቶ በተለይም በኢሳት ቴሌቪዠን ላይ በዶ/ር ፀሀይ የተሰጠው ትንተና እጅግ አስቂኝ ነው።  አባባሉን በደንብ ተከታትለን እንደሆን፣ „የውጭ ባንኮች ለኢትዮጵያ መንግስት ብድር የሚሰጡበት ዋናው ምክንያት እኛን ኢትዮጵያኖችን ስለሚወዱን ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በኢትዮጵያ መንግስት ስለሚተማመኑ ነው“፣  ብሎ ነው የእቅጩን የነገረን። ዕውነትም የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጓል፣ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ነው በለው ያምናሉ ወይ? አበዳሪ ባንኮችን ምን እንደገፋፋቸው አፍን አውጥቶ መቶ በመቶ ምክንያቱ እንደዚህ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም፣ ኢኮኖሚው በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ስላለ ነው ብድር የሚሰጡት የሚለው ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትና ምንነት፣ እንዲሁም ሰፋ ብሎ ስለተሚዋቀር የውስጥ ገበያ የማያውቅ ብቻ ነው እንደዚህ ብሎ አፉን ሞልቶ የሚናገረው። በእኔ ዕምነት ግን የውጭ ባንኮች ገንዘብ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያበድሩበት ምክንያት፣ 1ኛ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በአውሮፓ የማዕከላዊ ባንክና በአሜሪካኑ ፌድ እየታተመ በተጨባጭ ሲታይ በዜሮ ወለድ ባንኮችን የሚያደልብ ዶላርም ሆነ ኦይሮ  ይበተናል። እነዚህ የአሜሪካና የአውሮፓ የግል ባንኮች ከፊሉን ቁማር ሲጫወቱበት፣ የተቀረውን ደግሞ እንደኛ ላለው መንግስታት እንዲበደሩ አረንጓዴ መብራት ያሳዩታል። ካለምንም ወለድ ከማዕከላዊ ባንኮች የሚገኘው ብድር ባንኮች ውስጥ ካለስራ ከመቀመጥ ይልቅ አገሮችን ማሰስና የዕዳ ወጥመድ ውስጥ መክተት አለበት። በተለይም በአሁኑ ጊዜ በብዙ የአውሮፓ አገሮች የኢኮኖሚው ዕድገት እየቀዘቀዘ በመምጣቱና፣ የደቡብ አውሮፓ አገሮች አሁንም ቢሆን አስተማማኝ ሁኔታ ውስጥ ስለማይገኙና ሁኔታውም በዚህ ስለሚቀጥል የግል ባንኮች ብድር የሚሰጧቸውን አገሮች ማሰስ አለባቸው። በሌላ አነጋገር፣ የአገራችንን በዕዳ መተብተብ የምንረዳው ጠቅላላውን የግሎባል ካፒታሊዝምን ዕድገት የመረመርንና፣ በተለይም ደግሞ በተጨባጩ መስክና በፋይናንስ መሀከል ያለውን ሰፊ ሁኔታና፣ ፋይናንስ ካፒታል የራሱን ሎጂክ መከተል ከጀመረ ሰንበት ማለቱን የተረዳን እንደሆን ብቻ ነው። ይህም ማለት እ.አ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በፋይናንስ ገበያ ላይ የተፈጠረው ሁኔታና፣ ፈይናንስ ካፒታልም ከተጨባጩ የኢኮኖሚ ዘርፍ እየተላቀቀ በመምጣቱ የአየር በአየር ንግድ(Speculation) መጦፉና፣ „የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው“ በሚል ፈሊጥ የካፒታሊስት አገር ባንኮች የሶስተኛው ዓለም አገሮችን  በዕዳ መተብተብ ዋናው የሀብት ክምችት ዘዴና መሳሪያ ሆኗል። አሁንም በሌላ አነጋገር፣ በአሁኑ ጊዜ የፋይናንስ ካፒታል ከተጨባጩ የምርት ክንውን በመላቀቅ ትርፍ ለማካባት ሲባል እየሰፋና እያበጠ በመምጣት ደካማ አገሮችንም በዕዳ ወጥመድ ውስጥ እየከተታቸው ነው። ይህ ዐይነቱ መረን የለቀቀ የፋይናንስ ካፒታልም በራሳቸው በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረና፣ በደሀና በሀብታም መሀከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው እየመጣ ነው። ምክንያቱም ኢንቬስተሮች የሚባሉት ገንዘብ ከባንክ በመበደርና ከእነሱ ጋር በመመሰጣጠር፣ በተለይም በሬል ስቴት ላይ በመሰማራት አዳዲስ ቤቶች በመስራት ወይም ያሉትን በመግዛትና አድሶ በውድ በማከራየት በከተማዎች ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ እያስመረሩት ነው።

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ ዕዳውን ለመክፈል የግዴታ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በየዐመቱ ከምትለክውና ከምታስገባው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን ለዕዳው ክፍያ ማስተላለፍ አለባት። ይህ ማለት ደግሞ በዕዳው አማካይነትና መከፈል ስላለበት ጉዳይ ስናነሳ በዚህ መልክ ከውጭ ምንዛሪ የተወሰነው ለዕዳ ክፍያ የሚውል ከሆነ አገሪቱ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለመጀመር ቀርቶ ያሉትንንም ለማጠናቀቅና ለማካሄድ የማትችልበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው። አሁን ባለው የካፒታሊዝም ፖለቲካዊ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ የበላይነት ሌላ አገዛዝ ቢመጣ እንኳ ዕዳውን መክፈል አልችልም፤ ወይም ደግሞ ህጋዊ ያልሆነ አገዛዝ ነው የተበደረው ነው ብሎ እምቢ ማለት ስለማይቻል፣ ዕዳው የአንድ ትውልድ ሸክም ብቻ መሆኑ ቀርቶ ተከታታዩ ትውልድም የዕዳው ተሸካሚ እንዲሆን ይገደዳል። ይህም ማለት፣ ይህ አገዛዘ የተከተለውና የሚከተለው የተበላሸና አገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የባሰዉኑ መቀመቅ ውስጥ ነው የከተተን ማለት ይቻላል። ከዚህ  ስንነሳ የአገራችንን የዕዳ ክምችት በተራ የባንክ አሰራር ቴክኒክና ዕውቀት መረዳት በፍጹም አይቻልም። የተወሳሰበውን የግሎባል ካፒታሊዝምን ዕድገትና በደሀ አገሮች ላይ የሚያደርገውን ጫናና፣ በሱ መዳፍ ውስጥ ከቶ እንዲታሹና ዕድገታቸውም ቀጭጮ እንዲቀር  ከሚያደርገው ሂደት ጋር ብቻ ነው በአገራችን ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታና የዕዳውንም ዕድገት መረዳት የምንችለው።

በቃለ-ምልልሱ ከዕዳው ባሻገርም ስለ ውጭ መዋዕለ-ነዋይ(Foreign Direct Investment) ጨረፍ ጨረፍ ብሎ ተነስቷል። በተለይም መሬትን ለውጭ ከበርቴዎች ማከራየት፣ መፈናቀልን እስካላስከተለ ድረስ እደግፈዋለሁ በማለት ዶ/ር ፀሀይ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን አስፈላጊነት ነግሮናል። መሬት ለውጭ ከበርቴዎች በተሰጠበት አካባቢ ገበሬው ከቀዬው መፈናቀሉን እንዳልሰማም አድርጎ ነው የነገረን።

ያም ሆነ ይህ፣ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይን(Foreign Direct Investment) በሚመለከትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ስለሚኖረው ሚና በብዙዎቻችን ዘንድ የተምታታ አመለካከት አለ። ይህም የሆነበት ምክንያት፣ ስለ ህብረ-ብሄርና ስለ ህብረተሰብ አገነባብ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ለህብረ-ብሄር ግንባታ ስለሚኖረው ሚና ያለን አመለካከት ግልጽ ስላልሆነና፣ በዚህም ላይ ጥናት ስላልተካሄደ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን በሚመለከት በጅምላ ጠቀሜታ እንዳለው አድርገን ነው የምንቆጥረው። በአብዛኞቻችን ዕምነት ከውጭ የሚመጣ መዋዕለ-ነዋይ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለስራ መስክ መፈጠር አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ ባለፉት አርባና ሰላሳ ዐመታት በእርሻም ሆነ በኢንዱስትሪ ወይንም በሌላ ዘርፍ የሚካሄደውን የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰትና የዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎችን ሚና በሚመለከት በሰፊው ጥናት ተካሂዷል። የኒዎ ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች እንደዚህ ዐይነቱን የካፒታል ፍሰት ለዕድገት ያመቻል ብለው ሲሰብኩ፣ ትችታዊ አመለካከት ያላቸው ደግሞ አሉታዊ ጎኑን በማሳየት የሶስተኛው ዓለም አገሮችን ዕድገት እንዳቀጨጨ ለማሳየት ሞክረዋል። ብዙ ኢምፔሪካል ጥናቶችና በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፣ አብዛኛዎቹ ከጤናማ የህብረተሰብ ዕድገት ርቀው እንደሄዱና፣ ከውጭ በሚመጣ የመዋዕለ-ነዋይ አማካይነት ኢኮኖሚያቸው የባሰውኑ እንደተዝረከረከና የባህልም ድቀት እንደተጎናጸፉ እንገነዘባለን። በጥናቶቹም መሰረትና በየአገሮቹም ያለው ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው፣ በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚካሄደው የቀጥታ መዋዕለ-ነዋይ(Foreign Direct Investment) ክንውን ዋናው ዓላማ፣ 1ኛ) በርካሽ የሰው ጉልበት የጥሬ-ሀብትን ለማውጣት ወይም ተጨማሪ ምርትነት የሌለውን ምርት ለማምረት ሲሆን፣ 2ኛ) በዚህ አማካይነት የጥሬ-ሀብትን አውጥቶ እንዳለ ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ትርፍ ለማካበት ነው። ይህም ማለት የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዋና ዓላማ በየአገሮች ውስጥ የጥሬ-ሀብትን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ድረስ በማምረትና የስራ መስክ ከፍቶ የየአገሩ ገበያ እንዲያድግ ለማድረግ ሳይሆን፣ አገሮች ርካሽ የሰው ጉልበት አቅራቢ ሆነው እንዲቀሩና፣ ለዘለዓለምም የጥሬ-ሀብታቸውን ለመበዝበዝ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ከካፒታሊስት አገሮች ወይም ከቻይናና ከህንድ ወደ ሶስተኛው ዓለም በሚፈስበት ጊዜ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር እንጂ አገሮችን ከማሳደግና የተሳሰረ ህብረተሰብ እንዲገነባ ከማድረግ አኳያ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። እንደምናየው በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ እየተስፋፋና፣ የሚመረተውም ምርት በቀጥታ ውጭ እንዲወጣ እየተደረገ ነው። ገበሬውም ወደ ተራ ሰራተኛነት በመቀየርና የባርነት ደሞዝ እየተከፈለው መብቱን የተገፈፈበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ሰሞኑን ደግሞ በስዊድኑ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ሃ ኤንድ ኤም በሚባለው በአላሙዲን በኩል በኢትዮጵያ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን በደልና በአካባቢው ላይ ያመጣውንና የሚያመጣውን ጠንቅ አየተከታተለን ነው። እንዲሁም ቻይና የጫማ ፋብሪካ በመክፈትና ወዝ አደሩን በመመዝበር ወደ ተራ ታዛዥነት ውስጥ እንደከተተችው ሁኔታውን ለተከታተለ መገንዘብ ይቻላል። የመልቲ ናሽናል ኩባንያዎች በባንግላዲሽ ሴቶችና በተቀረው የአሺያ ሰራተኞች ላይ በሰባኛው፣  በሰማኒያኛውና በዘጠናኛው ዓ.ም ያደረሱትን በደል የቻይና ኩባንያዎች የአገራችን አገዛዝ በሰጣቸው መብት በመጠቀም ህዝባችንን ወደ ተራ በዝባዠነት በመቀየር ነፃነቱን እየገፈፉት ነው። ይህም ማለት ምን ማለት ነው ? በማንኛውም መልክ ይካሄድ፣ ማንኛውም አገር ይሳተፍበት የውጭ መዋዕለ-ነዋይ የአንድን አገር የውስጥ ገበያ በማስፋፋትና በማዳበር፣ እንዲሁም ኢኮኖሚውን አሳድጎ አንድ አገር ብሄራዊ ነፃነቷን እንድተቀዳጅ የማድረግ ብቃትነት የለውም። በመዋዕለ-ነዋይም አማካይነት የቴክኖሎጂ ዕውቀት በፍጹም ሊመጣ አይችልም። ሳይንስንና ቴክኖሎጂን እንዲሁም ዕውቀትን ያላካተተ መዋዕለ-ነዋይ ደግሞ በምንም ዐይነት ጤናማ ኢኮኖሚ እንዲገነባ የማድረግ ኃይል አይኖረውም። የሚገኘውም ትርፍ ወደ እናት አገር ወይም ኩባንያ ስለሚፈስ የተወሰነው ትርፍ እዚያው እንደገና ለመዋዕለ-ነዋይ በመዋል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳያመጣ ይታገዳል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣  በዋጋ ሽግግር ስሌት(Transfer Prise) መሰረት ከውጭ የሚመጡ መሽኖችና የመለዋወጫ ዕቃዎች ውድ ሆነው ተተምነው ስለሚገቡ የጠቅላላው የምርት ዋጋ ወደ ላይ እንዲወጣና፣ ትርፉ ትንሽ ሆኖ እንዲተመን ይደረጋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የውጭ ከበርቴዎች ለመንግስት ቀረጥ የማይከፍሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው። ባጭሩ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት ያለበትና በብሄራዊ የኢኮኖሚ ዕቅድ ውስጥ ተካትቶ መሰላት ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ በራሱና በህዝብ የሚተማመን አገር ወዳድ መንግስት ያስፈልጋል። አሁን ባለው የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ከማተረማመስና ከማዘበራረቅ አልፎ ህዝባችንን ወደ ባርነት ውስጥ እንደሚከተው አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በሌላ ወገን ግን ተቃዋሚ ነኝ በሚለውና በምሁሩ ዘንድ የዓለም ኩባንያዎችን ሚና በሚመለከት እስካሁን ድረስ የሚያመረቃ ጥናት አልተካሄደም።  በእኔ ዕምነት የዛሬውን አገዛዝ እቃወማለሁ፣ ለዕውነተኛ ኢኮኖሚና ለብሄራዊ-ነፃነት እታገላለሁ የሚል ሁሉ በግሎባላይዜሽን ስም የውጭ አገር ኩባንያዎች በአገራችን ምድር የሚጫወቱትን ሚና እያነሳ መወያየትና ወጣቱን ማስተማር አለበት። ይህንን ሳያደርግ ዝም ብሎ ብቻ በዲሞክራሲ፣ በመደብለ-ፓርቲና በሊበራል ዲሞክራሲ ስም ቢምልና ቢገዘት ችግሩ ተድበስብሶ እንዲቀርና ዕውነትኛ ነፃነትም እንዳይመጣ ከማድረግ በስተቀር አዎንታዊ ሚና ሊጫወት እንደማይችል መገንዝብ ይቻላል።

ከዚህ ስንነሳ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ እንዲሁም የዓለም ኮሙኒቲው የኢትዮጵያን አገዛዝ የተቀሩትን በመንግስት ስር ያሉትን፣ „የልማት አውታሮች“ የሚባሉትን እንደ ቴሌ ኮሙኒኬሽንና ባንክ እንዲሁም የመብራት ኃይል የመሳሰሉትን እንዲሸጥ ቢወተውቱ ለአገራችን ዕውነተኛ ዕድገት በማሰብ እንዳልሆነ መረዳት አለብን። እነዚህ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ድርጅቶች ቢሸጡና የውጭ ኢንቬስተሮችም ቢካፈሉ የተሻለ ኢንቬስት በማድረግ ቲኮኖሎጂያዊ ምጥቀትን በማምጣት የስራ መስክም ይከፍታሉ ማለት ዘበት ነው። ለምሳሌ የቴሌኮሙኒከሽንን ዘርፍ ብንወስድ፣ ይህ መስክ ለውጭ ኢንቬስተሮች ክፍት መሆኑ የባሰውን የተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲስፋፋ ከማድረግ በስተቀርና አገራችንን የተንቀሳቃሽ ስልክ ገበያ ከማድረግ ውጭ ለአገራችን ዕድገት የሚያመጣው ነገር ምንም ሊኖር አይችልም። ይህም ማለት በዚህ አማካይነት የቀረው ቋሚ ስልክ(Fixed Telefon) እንዲመታና መንገዱን ለተንቀሳቃሽ ስልክ ክፍት እንዲያደርግ ይገደዳል። ይህም ማለት ለዕድገት የሚጠቅመውንና የማባዛትም ባህርይ(Multiplier effect) ያለውን እንደ ኬብል ቴክኖሎጂዎችና ቋሚ የቤት ስልክ አገራችን ውስጥ እንዳይመረትና ቴክኖሎጂውንም የመማር ዕድል እንዳይኖር ይደረጋል። ከዚህም በሻገር ወደፊት እንደ ብሮድ ባንድ የመሳሰሉትን፣ ለተፋጠነ ኢንተርኔት ዳታዎችናን ድምጽን ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ በአገራችን ውስጥ እንዳይመረትና ተክኖሎጂውንም እንዳንማር እንታገዳለን። በሌላ ወገን ራሱ የወያኔ አገዛዝ ብዙ ቋሚ ስልኮችን እንዳፈራረሰና በተንቀሳቃሽ ስልክ እንደተካው ለማንኛችንም ግልጽ ነው። የተንቀሳቃሽ ስልኩንም ገበያ የሚቆጣጠሩት ራሳቸው የወያኔ ካድሬዎች ናቸው። ለኛ አስቸጋሪ የሆነውና የተምታታብን ጉዳይ የዛሬውን አገዛዝ ምንነትና ባህርይ በቅጡ አለመረዳት ነው። ከውጭ የሞባይል አምራቾች ጋር በመተባበርና ካድሬዎቹን እዚያው ልኮ እንዲሰለጥኑ በማድረግ የስልኩን መስክ እየተቆጣጠረ ነው። ስለሆነም ቴሌኮሙኒኬሽን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

ወደ ባንኩ መስክ ስንመጣም ተመሳሳይ ሁኔታ እንመለከታለን። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ የባንክ ስርዓት ኢንዱስትሪዎችን እንደየደረጃቸው ፈይናንስ ለማድረግ ሆኖ የተዘጋጀ የኢኮኖሚ መስክ አይደለም። በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ ቢያንስ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ፣ በተለይም ጀርመን አገር የተለመደ የባንክ አሰራርና የስራ ክፍፍል ዘዴና ድርሻ አለ። ይኸውም፣ 1ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ፣ የማዕከላዊ ባንኩንም ጨምሮ፣ 2ኛ) የህብረት ባንክ፣ 3ኛ) የግል ወይም የንግድ ባንኮች ናቸው። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮች በሙሉ በዝቅተኛ ወለድ ለትናንሽና ለማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም ቤት ለመስራት ለሚፈልግ ብድር የሚያበድሩ ናቸው። የማዕከላዊ ባንኩ ዋና ተግባር የገንዘብ ፍሰትንና የውጭ ከረንሲን መቆጣጠር ሲሆን፣ ከዚህ ባንክ የሚገኘው ትርፍ በቀጥታ ወደ ገንዘብ ምኒስተር ለበጀት ድጎማ ይተላለፋል። ይህ እስካሁንም የሚሰራበት የባንኪንግ ስርዓት ነው።  የንግድ ባንኮች ደግሞ ከህዝብ ዘንድ በቁጠባ መልክ የሚንቀሳቀሰውን የተወሰነውን በመሰብሰብና መልሶ በማበደር ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚጫወቱት ሚና አለ። ይሁንና በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ የንግድ ባንኮች ሚና ኢንዱስትሪዎችን በዝቀተኛ ወለድ ከመደጎም ይልቅ የበለጠ ትርፍ ለማካበት ሲሉ ወደ አየር በአየር ንግድ እንዳመዘኑ እንመለከታልን። የህብረት ባንኮችን ስንመለከት በህብረት ሙያ የተደራጁትንና አባል የሆኑትን ብድር በዝቅተኛ ወለድ የሚያበድር መስክ ነው። አብዛኛዎች የጋርዮሽ የኢኮኖሚና የሶሳል መስኮች የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በዚህ ባንክ አማካይነት ነው የሚተላለፉት።

ወደ አገራችን ስንመጣ ባንኮች ይሸጡ፣ ወይም ደግሞ የውጭ ኢንቬስተሮች ይሳተፉ ስንል ግልጽ ሆነው መቀመጥ ያለባቸው ነገሮች አሉ። ብድርን በዝቅተኛ ወለድ ለተጠቃሚውም ሆነ ለአምራቹ ሊሰጡ ይችላሉ ውይ? ባህርያቸውስ ይፈቅዳላቸዋል ወይ? የሚለውን ማውጣትና ማውረድ አለብን። እንዲያው ዶ/ር ዳንኤል እንደነገረን አንዳንድ የባንክ ሰራተኞች የውጭ ባንኮች መጥተው ቢካፈሉ ደስታውን አይችሉትም የሚለው አነጋገር እጅግ የዋህነት የተሞላበት ይመስለኛል። በአገራችን ያለው በባንኩ መስክ የሚታየው  ዋናው ችግር የወያኔ አገዛዝና ካድሬዎች የሚያደርጉት ጫና ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም ቢሆን በአማዛኙ ከእጅ ወደ አፍ በሚገኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ(Subsistence Economy) ስለሚገዛ ለካፒታሊዝም ዕድገት እንቅፋት ሆኗል ማለት ይቻላል። አብዛኛዎቹ ባንኮችም በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ ስለሚገኙ ከሰፊው ህዝብ ጋር ምንም ግኑኝነት የላቸውም። የህዝቡም የመቆጠብ ኃይል በጣም ደካማ በመሆኑና፣ ገንዘብም በባንክ አማካይነት ከአንዱ እጅ ወደ ሌላው ስለማይተላለፍ ባንኮች ለማበደር የሚችሉትን በቂ ካፒታል ለማግኘት አይችሉም። ስለሆነም ስለ ባንኩ መስክ  ድክመት በምናወራበት ጊዜ ችግሩን ከጠቅላላው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ማያያዝ መቻል አለብን። በካፒታሊስት ሎጂክ ላይ የተመሰረተ የሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚ እስካልተስፋፋ ድረስና፣ ሰፊው ህዝብም በቂ ገቢ አግኝቶ የመቆጠብ ኃይሉ ማደግ እስካልቻለ ድረስ የኢትዮጵያ ባንክ ስርዓት በውጭ ኢንቬስተሮች አማካይነት በተቀላጠፈ መልክ ይንቀሳቀሳል ማለት ዘበት ነው። የኢትዮያም እኮኖሚ በውጭ ባንኮች ተሳትፎ ያድጋል ማለት የግሎባል ካፒታሊዝምን ውስጣዊ ባህርይም አለመረዳት ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ የልማት አውታሮች ተብለው በሚጠሩት ንዑስ-መስኮች ዘንድ ለብዙዎቻችን ግልጽ ያልሆኑ መሰረታዊ ነገሮች አሉ። እነዚህ የልማት አውታሮች በመሰረቱ ምርት የሚመረትባቸው ሳይሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም አቅራቢዎች ናቸው። ሁሉም ማለት ይቻላል በ1950ዎቹ ዓ.ም ገደማ የተቋቋሙ ናቸው። እነዚህ የአገልግሎት መስጫዎች ሲቋቋሙ የአገራችን የኢንዱስትሪ መሰረት እጅግ በጣም ደካማ ነበር። በኋላም የምትክ ኢንዱስትሪ ሲስፋፋ፣ እነዚህን „ለህዝቡ ግልጋሎት“ ሊሰጡ ይችላሉ ተብለው የተቋቋሙትን የልማት አውታሮች ተብለው የሚጠሩትን በቴክኖሎጂ የሚደግፋቸውና አስፈላጊውን የመለዋወጫ ዕቃ የሚያቀርብላቸው የኢንዱስትሪ መስክ በአኳያቸው አልተስፋፋም። በሌላ አነጋገር የልማት አውታሮቹ በውጭ ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ የነበሩና፣ በዚህም ምክንያት የመስፋፋት ኃይላቸው ውስን ነበር።  ስለሆነም እንደ ናሙና የተቋቋሙና በተወሰነ ቦታም የተተከሉ በመሆናቸው ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝባችን ከነዚህ የልማት አውታሮች እየተባሉ ከሚጠሩት የተገለለ ነበር፤ አሁንም ነው ማለት ይቻላል። እንደ አየር መንገድ የመሰለው ደግሞ ይበልጥ የተገለለ ኢኮኖሚ(Enclave Economy) ባህርያ ያለውና፣ ከውስጥ የምርት ክንውን ጋር የተሳሰረ አይደለም። ከዚህ ስንነሳ በምን ምክንያት እነዚህ ንዑስ-መስኮች  የልማት አውታሮች ተብለው እንደሚጠሩ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው።

ያም ሆነ ይህ በመንግስት ስር ያሉትን ድርጅቶች ወደ ግል መዘዋወር አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጀት የመሳሰሉት ስለወተወቱ ግራ የሚያጋባን ነገር ሊኖር በፍጹም አይችልም። ከላይ እንዳልኩት በጀርመን ምድር ከባንኩ ባሻገር፣ የባቡር ኩባንያ እንዳለ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው ያለው። በትርፋማነትና በተቀላጠፈ መንገድም የሚሰራ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃትነት አላቸው ከሚባሉ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ነው። አውቶኖመስ ሆኖ የሚሰራና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚንቀሳቀስ ነው። መንግስት በፖስታና በቴሌኮሙኒኬሽን ውስጥ ከፍተኛ ድርሻውን ይዟል። በአንፃሩ እነዚህን የመሳሰሉ ድርጅቶች ወደ ግልነት በተሸጋገሩባቸው እንደ እንግሊዝ በመሳሰሉት አገሮች የባቡር ኩባንያዎች ከገዙ በኋላ ትርፋማ አይደሉም ያሏቸውን በሙሉ በማውደም ህዝቡን ችግር ውስጥ እንደከተቱት ይታወቃል። ከአደጋም አንፃር እጅግ አስቸጋሪዎች እየሆኑ እንደመጡ ይታወቃል። ከዚህ ስነንሳ ሁሉም ነገር በነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ህግ ቢካሄድ የተቀላጠፈ አሰራር ሊኖር ይችላል የሚለው ተራ አነጋገር ብዙም ወደፊት የሚያራምደን አይሆንም። መነሳት ያለበት ጉዳይ በመንግስት፣ በህብረትና በግል ባለሀብታሞች መሀከል ሊኖር የሚችለውን የስራ ክፍፍል በህግ መከለልና፣ መንግስትም የኢኮኖሚውን ዕድገት አጋዠ እንዲሆነ ማስተማርና በህግ  በሚገባ ማስቀመጥ ይቻላል። የመንግስት ሀብት ሲባልም የህዝብ ሀብት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በዚህ ዐይነቱ የስራ ክፍፍልና መደጋገፍ የተሻለና ለሰፊውም ህዝብም የስራ ዕድል ለመክፈት የሚያስችል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መዘርጋት ይቻላል። በሌላ ወግን ግን በመንግስት ስር ያሉ የአገልግሎት መስጫ ኩባንያዎች የግዴታ ከትርፍ አንፃር መስራት የለባቸውም። መመዘን ያለባቸው ለህዝብ ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንፃር ሲሆን፣ የምርትን ዋጋ መሸፈን በሚለው መርሆ መሰረት ቢንቀሳቀሱ በቂ ነው።  ያም ሆነ ይህ እነዚህን መስኮችም ሆነ የጠቅላላውን ኢኮኖሚ ሁኔታ በሚመለከት የፖለቲካው ጥያቄ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው። መንግስትና አገዛዝ፣ አገዛዝና ኢኮኖሚ በአንድነት በተዋቀሩበት አገርና፣ ለማንኛውም አምራችና የአገልግሎት አቅራቢ ኃይል መፈናፈኛ በማይሰጡበት አገር ስለ ልማት አውታርነትና ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም። በሌላ አነጋገር ለአንድ አገር ዕድገት ዲሞክራሲያዊና ከውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት መኖር ወሳኝ ነው። የሚደረገውም ትግል ይህንን አስቸጋሪ ነገር መስመር ለማስያዝ ነው።

         ለአገራችን መፍትሄው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ወይስ ሌላ የኢኮኖሚ ፖሊሲ !!

ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ በቃለ-ምልልሱም ሆነ  ቀደም ብሎ ለድህረ-ገጾች በላከው ጽሁፉ ላይ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲን አማራጭ የሌለውና ለአገራችንም የተወሳሰበ ችግር እሱው ብቻ መፍትሄ እንደሆነ ነው ሲያስተምረንና ሲሰብክ የነበረው። እንደምገምተው ከሆነ በዚህ ላይ የማያወላዳ አቋም ነው ያለው። ይሁንና ግን  የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በአገራችን ምድር ላይ እንዴት እንደሚመነዘር በዝርዝር አላስረዳንም። በጽሁፍም በሰፊው በጥናት ያቀረበበት ቦታ የለም። ይህ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ አሜሪካን አገር የነፃ ገበያ ስለተካሄደ ነው እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ቢለን በፍጹም ሊያሳምነን አይችልም። የአሜሪካን የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክም ዶ/ር ዳንኤል እንደሚለን የተከናወነና እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ አይደለም።  በትምህርት ቤትና በዩኒቨርሲቲዎች ለመማሪያ በቀረበው የኢኮኖሚክስ መጽሀፎች አማካይነትም የአሜሪካን ካፒታሊዝም በፍጹም አልተገነባም። መጽሀፉ ያስተማረን እንደዚህ ነው፣ ኢኮኖሚውም በዚህ መልክ ነው የተገነባው የምንባል ከሆነ የዓለም የህብረተሰብ ታሪክ በአዲስ መልክ መጻፍ ያለበት ይመስለኛል።

በአውሮፓው ታሪክም ውስጥም ሆነ በአሜሪካና በሌሎች በተሳኩ አገሮች ውስጥ የከበርቴው መደብ በአሸናፊነት እስከወጣ ድረስ ሰፊውን ህዝብ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች፣ ለከተማና ለመንደር ግንባታዎች፣ ለካናልና ለድልድይ ስራ… ወዘተ. በማንቀሳቀስ ነው ለካፒታሊዝም መሰረቶች የተጣሉት። የአውሮፓው ኢኮኖሚ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከፈራረሰና ቤቶችም ከወደሙ በኋላ ጦርነቱ ሲያበቃ የአውሮፓ መንግስታት በነፃ ገበያ ብቻ ነው ኢኮኖሚውን መገንባት የሚቻለው ብለው ተዓምር ይጠበቁ አልነበረም። ልዩ የመገንባት ዕቅድ በማውጣት፣ የሰውን ኃይልና የነበረውን ፖቴንሺያል ሀብት በማንቀሳቀስ የተንኮታከተውን ኢኮኖሚያቸውንና ከተማዎቻቸውን በሃያ ዐመታት ውስጥ መልሰው መገንባት ችለዋል። በዲሲፕሊንና በተጠናከረ ድርጅታዊ አሰራር በመመራት፣ ግለሰብአዊ ኃላፊነትን ከህብረተሰብአዊ ኃላፊነት ጋር በማጣመር ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ የተወሳሰበ ኢኮኖሚ መገንባት የቻሉት። ወደ ሁለቱም የኮሪያ አገሮች  ስንመጣም፣ ሁለቱም ኢኮኖሚያቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ከተማዎቻቸውም እንዳሉ የወደሙ ነበሩ። ከብረት ጥንካሬ ባላነሰ ዲሲፕሊንና ድርጅታዊ አሰራር ብቻ ነው ኢኮኖሚያቸውን መልሰው መገንባትና ህዝቦቻቸውን መመገብ የቻሉት። ስለዚህም የገበያ ኢኮኖሚ እያሉ ከመወትወት ይልቅ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ አገሮች እንዴት ህብረተሰቦቻቸውንና ኢኮኖሚያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ መገንባት ቻሉ? ብሎ መጠየቅና ማጥናት የማንኛውም አገር ወዳድ ግዴታ መሆን ያለበት ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ፣ የአገራችን የተወሳሰበ ችግር  በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው ማለት ከፍተኛ  የዋህነት ብቻ ሳይሆን አውቆም ሆነ ሳያውቁ  ችግሩ እንዳይፈታ መንገዱን መዝጋት  ነው። በመጀመሪያ፣ ነፃ ገበያ የሚባል ነገር የለም። በማንኛውም አገር ሁሉም ነገር በህግ የታሰረና ከህግ አንፃር የሚካሄድ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በነፃ ገበያ አማካይነት በአንድ አገር ውስጥ ያለ ህዝብ በዕኩል ደረጃ የሀብት ተካፋይ ሊሆን አይችልም። የነፃ ገበያ አለ በሚባልባቸው በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በሙሉ እስከ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆነ ሀብት 5-10% በሚሆነው ህዝብ ቁጥጥር ስር ያለ ነው። አብዛኛው ህዝብ ተቀጥሮ የሚሰራና በደሞዝ የሚተዳደር ነው። ስለዚህም ስለ ነፃ ኢኮኖሚ ማውራት በፍጹም አይቻልም ማለት ነው። የአገራችንን ችግር ወደ መፍታቱ ስንመጣ የካፒታሊስት አገሮች ወደዚህ ደረጃ የደረሱት የነቃ ፖሊሲ በማካሄድ እንጂ ችግሩን የገበያ ኢኮኖሚ ይፈታዋል፤ ሁሉንም ነገር ለገበያ ተዋናዮች ልቅ አድረገን እንተው በማለት አይደለም። አንድ ቦታ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ የተለያዩ ደረጃዎችን አልፎ እንደመጣ ነው። በአሁኑ ውቀት ግሎባል ካፒታሊዝም፣ በተለይም በፋይናንስና በፍጆታ አጠቃቀም መልክ የሚገለጸው የምርትና የንግድ ክንውን የካፒታሊዝም ዋናዋቹ ገጽታዎች ናቸው። የኛም ዕድል በሱ የሚወሰን ነው።

ከዚህ ባሻገር ዶ/ር ዳንኤል የመሬትን መሸጥና መለወጥ ጉዳይ ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያለውን ሚና በማንሳት ይናገራል። የመሬትን መሸጥና መለወጥም ዋናው የዕድገት መሰረት አድርጎ ለማቅረብም ይሞክራል። አሁን ባወጣው ጽሁፉም ይህንን ነው የሚያረጋግጥልን። እዚህ ላይ ግን ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ ግልጽ ያላደረጋቸው ነገሮች አሉ። 1ኛ) መሬት ይሸጥ ይለወጥ በሚባልበት ጊዜ ተራው ገበሬ ገንዘብ ከየት አምጥቶ ነው መግዛት የሚችለው፤ 2ኛ) መሬትን ማነው የሚሸጠው? 3ኛ) ከሽያጭ የሚገኘውስ ገቢ ለምንድን ነው የሚውለው ? የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ጉዳዮች ይመስሉኛል። የመሬትን መሸጥ መለወጥ የተመለከትን እንደሆን፣ እ.አ ከ1989 ዓ.ም በአንድ ቅጽበት ከሶሻሊስት ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እንሸጋገራለን ብለው የመንግስትን ሀብት፣ መሬትንም ጨምሮ በመሸጥ ወደ ግልሀብትነት እንዲለወጥ ያደረጉ አገሮች ወደ ተስተካከለና ሰፊውን ህዝብ ወደ ሚጠቅም የኢኮኖሚ ስርዓት አልተሸጋገሩም። በቀድሞዎቹ የሶሻሊስት አገሮችና በቻይናም ጭምር የመሬት መሸጥ መለወጥ ከፍተኛ የሆነ የህዝብን መፈናቀልንና የአየር ባየር ንግድን ነው ያስከተለው። የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አካሂደናል ባሉ አገሮች በሙሉ ድህነት ተስፋፍቶ ብዙ ሰዎች ወደ ውጭ በመውጣት ላይ ናቸው። ከዚህ ስንነሳ የመሬት መሸጥ መለወጥ ገበሬውን የሚጎዳና የባሰውኑ ከመሬቱ የሚያፈናቅል ነው። በእኔ ዕምነት የመሬት ጉዳይ ለገበሬው በይዞታ(Possession Right) መሰጠት ያለበትና፣ ከአባት ወደ ልጅም እንዲተላለፍ የሚደረግበት ህጋዊ ሁኔታ በመፍጠር መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የመሬት አያያዝና ጥበቃ ጉዳይ እንደዚሁ ተጠንቶና በህግ መልክ ጸድቆ ገበሬው መሬቱን በስርዓት እንዲያርስ ማድረግ ነው። የመሬትን ጥያቄ በይዞታ መልክ መፍታቱ በራሱ የአገራችንን የምግብ እጥረትና አጠቃላዩን የኢኮኖሚ ችግር የሚፈታ አይደለም። ገበሬው የግዴታ ኢንስቲቱሽናላዊ ድጋፍ ማግኘት አለበት። ከዚህም በላይ ለገበሬው እጅግ በዝቅተኛ ወለድና ከረዠም ጊዜ አንፃር ብድር እንዲከፈል የሚያደርግ ልዩ የባንክ አገልግሎት መስጫ ድርጅት ማቋቋም ወሳኝ ነው። በተጨማሪም ለእርሻ ተግባር የሚያገለግሉ ትናንሽ የማምረቻ መሳሪያዎችን የሚያመርቱና ለገበሬው የሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች መትከል ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። እንደሚታወቀው እርሻ በራሱ የሀብት ክምችት መፍጠሪያ ሊሆን በፍጹም አይችልም። በቴክኖሎጂ ሲደገፍና፣ የሰፊውም ህዝብ የመግዛት ኃይል እየጨመረ ሲመጣ የገበሬውም ገቢ ያድጋል ሊያድግ ይችላል። በዚህ ዐይነት ትስስርና የንግድ ልውውጥ ብቻ ነው የአንድ አገር ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው።

በእርሻው መስክ የሚታየው ችግርና የእህል እጥረት በዚህ ብቻ የሚፈታ አይደለም። የህብረት እርሻም መቋቋም ሌላው አንደ መፍትሄ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። የህብረት እርሻንም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ክንዋኔዎችን በሚመለከት በካፒታሊስ አገሮች የሚሰራበት ስለሆነ ይህንን ከሶሻሊስት ስርዓት ጋር እያያዙ ህዝብን ማስፈራራት አስፈላጊ አይደለም። ከዚህ በላይ በመለስተኛና ከፍ ባለ መልክ በራሳቸው ካፒታል ለማረስ ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ከበርቴዎች መሬትን በትንሽ ኪራይ ማከራየት ይቻላል። በሌላው ወገን  የመንግስትን ገቢ፣ በገቢ ታክስ ማስተካከል ይቻላል። ስለሆነም ዶ/ር ዳንኤል እንደሚለው ሳይሆን፣ የመሬት ጥያቄ ጉዳይ ከጠቅላላው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር መታየት ያለበትና መፈታትም ያለበት ጉዳይ ነው። መሬት መሸጥ መለወጥ አለበት የሚለው የማያቋርጥ ውትወታ ውዠንብርን ከመንዛት በስተቀር ለችግራችን ፍቱን መፍትሄ ሊሰጠን የሚችል አይደለም።

ያም ሆነ ይህ፣ የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት የምንፈልግ ከሆነ የፖለቲካው ጥያቄ መስመር መያዝ አለበት። አገር አፍራሽ አገዛዝና የተጣመመ የፖለቲካ አመለካከት ባለበት አገር ውስጥ ስለ ነፃ ገበያም ሆነ ስለ ሌላ ዐይነት ፖሊሲና ስርዓት ማውራት በፍጹም አይቻልም። ይህም ማለት አገራችንና ህዝባችን ከዚህ ዐይነቱ ኋላ-ቀር አገዛዘ መላቀቅና ህዝባችንም ዕውነተኛ ነፃነቱን መቀዳጀት አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ዕውነተኛ ዕድገትን ሊያመጣ የሚችል በመንግስት የተደገፈና ህዝቡም የሚሳተፍበት፣ እንዲሁም ደግሞ የአገሪቱን ሀብት በስርዓት ለማንቀሳቀስና ለዕድገት እንዲያመች ሆኖ የሚዘጋጅበት ሁኔታ ይፈጠራል። በተለይም በሚቀጥሉት አርባና ሃምሳ ዐመታት ህዝቡን በሙሉ ያላካተተና ያላሳተፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመረቃ ውጤት ሊያመጣ በፍጽም አይችልም። ያለውም መወናበድና መሰረታዊም ጥያቄ እዚህ ላይ ነው። በሌላ አነጋገር በግለሰብ ተሳትፎ ብቻ ነው የአገራችን ችግር ሊፈታ ይችላል ማለት ድህነቱ ዘለዓለማዊ ሆኖ ይቅር እንደማለት ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ካፒታሊዝም ዕድገት ያለማወቅም ነው።

ከፖለቲካ ጥያቄ ባሻገር በተለይም የመሬት ጥያቄና ሌሎች ሀብቶች መፍትሄ ማግኘት አለባቸው። የየካቲቱ አብዮት ያነሳው ጥያቄና በተግባር ላይ በመመንዘር የነበረው ገበሬውን የመሬት የይዞታ ባለቤት የማድረጉ ጥያቄ  በጊዜው በነበሩ ፀረ-ዲሞክራሲና የፀረ-ዕድገት ኃይሎች ሊቀለበስ ችሏል። በዚህ አገዛዝ ዘመን ደግሞ ገበሬው ማዳበሪያ እንዲገዛ በመገደድና በዕዳ በመተብተብ ፍዳውን እንዲያይ ተደርጓል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ዘመናዊ ፊዩዳሊዝም በመስፋፋት ገበሬው ከመሬቱ እየተፈናቀለ ነው። ከዚህም በላይ  በሊዝ „ ለውጭ ከበርቴዎች“ የሚሰጠው መሬት ገበሬውን ማፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ቀን ሰራተኛነት በመቀየር እንዲበዘበዝና በኑሮው እርግጠኝነት እንዳይሰማው አየተደረገ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በከተማዎች፣ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ በአገዛዙና በካድሬዎች ኗሪውን ህዝብ አርባና ሃምሳ ዐመታት ያህል ከኖረበት እያፈናቀሉ ቤቶች በመስራት አዲስ የህብረተሰብ ግኑኝነት የተፈጠረበትና የሚፈጠርበት ሁኔታን እንመለከታልን። በሌላ አነጋገር፣ ልክ እንደገጠሩ መሬት የከተማ ቦታም ለሰፊው ኗሪ ህዝብ መሬት በርካሽ ዋጋ ተከራይቶ ቤት የሚሰራበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በተጨማሪም  በጉልበትና ያለ አግባብ የተነጠቁ መሬቶች ወደ መንግስትና ወደ ባለቤቱ የሚመለሱበት ሁኔታ መጠናት ያለበት ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።  እንደሚታወቀው የዛሬው የአገራችን ሁኔታ ከዘመነ ፊዩዳሊዝም የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም። ይህም ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ለአዲስ የመንፈስና የባህል ተሃድሶ አብዮት በመንቀሳቀስ እጅ ለእጅ በመያያዝ አዲስና የተከበረች አገር ለመገንባት መነሳት አለበት። የለም በምርጫ ብቻ ነው ያለውን ሁኔታ መቀየር የምንችለው የምንል ከሆነና የውጭ ኃይሎችንም የምንማፀን ከሆነ የባርነቱ ዘመን ይራዘም እንደማለት ይቆጠራል። መልካም ነባብ !!

                                                                            ፈቃዱ በቀለ

                                               fekadubekele@gmx.de