[gtranslate]

አንድ ህብረተሰብ ወይም ማህበረሰብ ሊተሳሰርና ሊጠነክር የሚችለው አገዛዙ ተግባራዊ

በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው !!

                                                            ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

    08.11.2019

 

 

መግቢያ

ዛሬ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና አገራችንንም ጨምሮ በግልጽ የሚታዩትን የተወሳሰቡ ችግሮች ስንመለከት የችግሮቹ  ዋናው ምንጮች በስልጣን ላይ ያሉት አገዛዞች እንደሆኑ መገንዘቡ ከባድ አይደለም። አገዛዞች የመንግስቱን መኪና፣ ማለትም የሚሊታሪውን፣ የሲቪል ቢሮክራሲውን፣ የፀጥታውንና የፖሊሱን ስለሚቆጣጠሩ በዚህም አማካይነት የህዝቦቻቸውን ዕድል በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልክ ይወስናሉ። ይህ ጉዳይ ደግሞ ሊወሰን የሚችለው ባላቸው ንቃተ-ህሊናና የዕውቀት ዐይነት ነው።

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የአገራችንና የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የህብረተሰብ አወቃቀር ከአውሮፓው የህብረተሰብ አወቃቀር መለየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪካቸውም በእነሱ ሊወሰን ችሏል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች፣ አገራችንንም ጨምሮ አንድ ህብረተሰብ እንደማህበረሰብ ሊኖር የሚያስችሉትን መሰረታዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ነገሮችን ማሟላት አልቻሉም። አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች በጥሬ-ሀብትና በእርሻ ምርት በመመካታቸውና፣ ይህንንም ዋናው የገቢ ምንጫቸው በማድረጋቸው ከሰማንያ በመቶ የሚሆነው ህዝብ አስተማማኝ ገቢ የለውም። ጥቂቶች የተንደላቀቀ ኑሮ ሲኖሩ አብዛኛው ህዝብ አንድ ሰው ለመኖር ከሚያስችለው የገቢ ገደብ በታች ነው የሚያገኘው። በየአገሮች ውስጥ የተተከሉት እዚህ ግባ የማይባሉ ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት መስኮች በጥቂት ከተማዎች ብቻ የሚገኙ በመሆናቸው አብዛኛው ወጣትና ህዝብ ወደ ከተማዎች በመጉረፍ ከተማዎችን በማጣበብ ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም በዋና ከተሞች ከፍተኛ መጨናነቅ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከቤት እጦትና ከመጸዳጃና እንዲሁም ከንጹህ ውሃ ጉድለት የተነሳ አብዛኛው ህዝብ ለበሽታ የተጋለጠ ነው። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚታዩባቸው ይሆናሉ። መንግስታትም በቀላሉ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎትና የስራ ዕድልን የማግኘት ጉዳይ ማሟላት ስለማይችሉ  የህዝባቸውን ጥያቄና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ተቃውሞ በአመጽ ብቻ ሊመልሱ የሚሞክሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

እንደሚታወቀው አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና አገራችንንም ጨምሮ በታሪካቸው ውስጥ የፖለቲካ ኢኮኖሚክስ፣ የሶስዮሎጂ፣ የሳይንስና የፍልስፍና መሰረት ስሌላቸው የየአገራቸውን ችግሮች ለመቅረፍና የህዝባቸውን ፍላጎት ለማርካት ፍቱን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ማውጣት አልቻሉም። የአለፈውን የሃምሳ ዐመታት የአፍሪካ አገሮችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ አብዛኛዎች ፖሊሲዎች ከውጭ የመጡ ናቸው። ፖሊሲዎቹ በሙሉ ከየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የተነደፉ ባለመሆናቸው ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ ፍቱን መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የባሰውኑ ህብረተሰቦችን እያዘበራረቁ ናቸው። የችግሩን ዋና ምንጭ ለመጠየቅ የሚቃጣ የተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴና የሲቪል ማህበረሰብ በየአገሩ ባለመኖሩ ከውጭ የሚመጡ ኤክስፐርቶች፣ በተለይም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ አማካሪዎች በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ስለሚመክሩና ጫና ስለሚያደርጉ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት አልቻሉም። የባሰውኑ በውጭ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው የተነሳ ለህዝቦቻቸው አለኝታ ሊሆን የሚችል የኢኮኖሚ አውታር በአገር አቀፍ ደረጃ ሊዘረጉ አልቻሉም። በተጨማሪም በዕዳ በመተብተብና የወለድ ወለድ በመክፈል ሀብት ወደ ውጭ እንዲፈስ ከማድረግ በስተቀር የየአገሮቻቸውን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ሊገነቡ በፍጹም አልቻሉም። ለአብዛኛዎቹ አገሮች የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብት ለጠንካራ የኢኮኖሚ መገንቢያ መሰርት ከመሆን ይልቅ በራሱ ችግርን ፈጣሪና ድህነትን አስፋፊ ነው የሆነባቸው።

እኛ በአውሮፓ ለረጅም አመታት የምንኖር ኢትዮጵያውያን ምሁሮች የአገራችንና የሌሎች አፍሪካ አገሮችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከአውሮፓው የህብረተሰብና የኢኮኖሚ አገነባብ ታሪክ ጋር ከአወዳደርን በኋላ የደረስንበት ድምዳሜ በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያለው ሁኔታ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት ነው። እንደሚታወቀው እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን የማሰብና የመፍጠር፣ እንዲሁም የኑሮውን ሁኔታ የመለወጥ ኃይልና ችሎታ አለው። በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ህዝብ በትክክለኛ ፖሊሲ ከተመራና እንዲተባበር ከተደረገ በአገር ውስጥ ባለው ሀብት ማደግና ጠንካራ አገር መገንባት ይችላል። ጠንካራና የተከበረ አገርን የመገንባቱ ጉዳይ ምንም ወይም ጥቂት የጥሬ-ሀብት ብቻ ያላቸው እንደ ጃፓን፣ ቻይና፣ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር የመሳሰሉት አገሮች አረጋግጠውልናል። ይሁንና ግን አብዛኛዎች የአፍሪካ አገዛዞች የህዝቦቻቸውን ፍላጎትና ህልም ከማስቀደምና የምሁሮቻቸውን ምክር ከመስማት ይልቅ የዓለም ኮሙኒቲውን ምክር በመስማት በየጊዜው ወደ አዘቅት እየወረዱና ህዝቦቻቸው አቅመ-ቢስ ሆነው እንዲቀሩ እያደረጉ ነው። ከዚህ ስንነሳ የአገራችንን አስቸጋሪና አስቀያሚ ሁኔታ ለመለወጥ በእርስዎ የሚመራው መንግስት የግዴታ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አለበት። በአገራችን ውስጥ ህዝብን የሚጠቅምና አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማስገነባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ቀደም ያለው የአገራችን አገዛዝ እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ መመርመር አለብን። ከዚህ ስንነሳ በእርግጥ ከእርስዎ በፊት የነበረው አገዛዝ እስከዛሬ ድረስ የአብዮታዊ ዲሞክራሲና የልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ወይ ተግባራዊ ያደረገው? የሚለውን ጥያቄ የግዴታ መመለስ ይኖርብናል። ይህ ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ የሚቻለው።

አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው ?

በመጀመሪያ አብዮት የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ እንመልከት። አብዛኛውን ጊዜ አብዮት የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ ከኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር ሲያያዝ፣ የኢንዱስትሪ አብዮት በመባል በሁላችንም መንፈስ ውስጥ ሊቀረጽ ችሏል። ይሁንና በኢኮኖሚክስ የታሪክ ተመራማሪዎች ዕምነት የኢንዱስትሪ አብዮት ከመቅጽበት የተካሄደ ሳይሆን አንድ ሰው በፈጠረው ቴክኖሎጂ ላይ ሌላው በመቀጠልና በማዳበር ወይም በማስፋፋት በአንድ ወቅት የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የታየበት እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም ተሰበጣጥረው የተለያዩ ምርቶችን ያመርቱ የነበሩ ትናንሽ እንዱስትሪዎች በአንድ አጠቃላይ የአመራረት ስልት በመደራጀት ወደ ፋብሪካነት የተለወጡበትና፣ ከዚያ በፊት የትናንሽ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት የነበረው ራሱ ወደ ሰራተኛነት የተለወጠበትን ሁኔታ የኢንዱስትሪ አብዮት ብለው  ይጠሩታል።

ወደ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ስንመጣም የመጀመሪያው አብዮት የተካሄደው እ.አ በ1640 በእንግሊዝ አገር ሲሆን፣ ዕድገትን በሚፈልገው በአዲሱ የከበርቴ መደብና የሊበራል አስተሳሰብ ባላቸው ምሁራን በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፋፊ መሬቶችንና የመንግስትን መኪና በሚቆጣጠረውና ለውጥን በማይፈልገው በአሪስቶክራሲው መደብና በንጉሱ መሀከል ነበር። ከ20 ዓመት የርስበርስ ጦርነት በኋላ የከበርቴው መደብና ሊበራል ኃይሎች በአሸናፊነት በመውጣት ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥሩ ችለዋል። ሁለተኛው አብዮት ደግሞ  እ.አ በ1789 ዓ.ም በፈረንሳይ አገር የተካሄደ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ያረጀውንና ዕድገትን የሚቀናቀነውን  በንጉስ ሊውስ 16ኛ የሚመራውን ኋላ-ቀር አገዛዝ አሽቀንጥሮ የጣለ አብዮት ነበር። አብዮቱ አሰቃቂ ቢሆንም ለአዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በር የከፈተና ፈረንሳይን ወደ ህብረ-ብሄር እንድታመራ ያደረገ ነው።  በሶስተኛ ደረጃ፣ ሰፋ ባለመልክ በኮሙኒስቶችና በሶሻል ዲሞክራቶች በመመራት በጀርመን ምድር በ1848 የተካሄደው አብዮታዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ይህ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአውሮፓ አገሮችን ያዳረሰ ነበር።  በወቅቱ የወዝአደሩ መደብ ቀስ በቀስ እየተደራጀና ለመብቱ መታገል እንዳለበት የተገለጸለት ነበር። ይህም ሊሆን የቻለው በጊዜው የወዝአደሩ መደብ በቀን ከአስራ ሁለት ሰዓት በላይ ይሰራ ስለነበረና፣ የህፃናትም ስራ የተስፋፋ ስለነበር ወዝአደሩ የግዴታ የስራ ሰዓት እንዲቀነስ ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲያዊ መብቶች በመታገል የራሱን አገዛዝ ለመትከል የሚንቀሳቀስበት ዘመን ነበር። በተለይም እንደጀርመን የመሳሰሉት አገሮች በአምባገነናዊ የሞናርኪስቶች አገዛዝ የተነሳ የዲሞክራሲ ነፃነቶች የታፈኑበት ዘመን ስለነበርና፣ ከፍተኛም ብዝበዛ በመካሄዱ ይህንን ለመግታት ሲባል የግዴታ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ሊካሄድ ቻለ። ይሁንና ግን እንቅስቃሴው ሊከሽፍ ሲችል፣ እነቢስማርክ የማህበራዊ መሻሻል ህጎችን በማውጣት በኮሙኒስቶችና በሶሻል ዲሞክራቶች የሚመራውን እንቅሳቅሴ ሊያኮላሹት ችለዋል። በቢስማርክም የማህበራዊ ፖሊሲ አማካይነት አጠቃላይ የህክምና ኢንሹራንስ፣ የጡረታ አበልና ሌሎች የማህበራዊ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በመሆን ወዝአደሩ የዕድገት ተካፋይ ሊሆን በቅቷል። በፖሊሲው መሰረትም የኢንዱስትሪና የንግድ ባለሀብቶች በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሰራተኛው መደብ እኩል  በማዋጣት የማህበራዊ መስኩን እንዲደጉሙ ተደርገዋል። ይህ ዐይነቱ የቢስማርክ የማህበራዊ ፖሊሲ እስከዛሬ ድረስ የሚሰራበት ነው።

በአራተኛ ደረጃ፣  እ.አ በ1917 ዓ.ም  በራሺያ ምድር የተካሄደው አብዮት ነው።  የራሺያ አብዮት እነሌኒን በሚመሩት በቦልሺቢኪ ፓርቲ  የተካሄደና ግቡንም የመታ ሲሆን፣ ከራሺያ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖም ነበረው። ለአብዮቱም ዋና ምክንያት የዛር መንግስት እስከዚያ ጊዜ ድረስ አስፈላጊውን የጥገና ለውጦች ለማካሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው። ንጉሱና ቤተሰቦቹ በተደንላቀቀ ሁኔታ ሲኖሩ፣ ሰፊው የራሺያ ህዝብ ደግሞ በድህነትና በረሃብ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነበር። ይህ ሁኔታና፣ በተለይም ደግሞ ከ1914-1918 ዓ.ም የጀርመን ወራሪዎች በራሺያ ላይ በከፈቱት የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት አገዛዙ ተዳክሞ ስለነበር እነሌኒን ይህንን ተጠቅመው በ1917 ዓ.ም የጥቅምትን አብዮት አወጁ። በዚህም የተነሳ የጦርነት ኮሙኒዝም የሚባለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማወጅ በጦርነቱ ምክንያት የደቀቀውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎች ተወሰዱ።  በግል ይዞታ ስር የሚገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎችንና ኢንዱስትሪዎችን በመንግስት ቁጥጥር ስር በማዋል፣ በተለይም የእርሻው ዘርፍ ተጨማሪ ምርት(Surplus Product) ያመርት ዘንድ አስፈላጊው እርምጃዎች ተወሰዱ። ይሁንና ይህ ፖሊሲ እንደተጠበቀው ውጤታማ ባለመሆኑ፣ እነ ሌኒን ይህንን የጦርነት ኢኮኖሚ ፖሊሲ  በአዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመተካት የገበያ ኢኮኖሚ ሊስፋፋና ሊዳብር የሚችልበትን ሁኔታ አመቻቹ። በአዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረትም(New Economic Policy)፥ ትናንሽ የንግድ መደብሮችና(Retail Trade)፣ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በግል ይዞታ ስር እንዲውሉ ሲደረግ፣ ባንኮች፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ የውጭው ንግድ፣ የመንገድና የመገናኛ መመላለሻዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲቀሩ ተደረገ። አብዮቱ እስከፈነዳና እነዚህ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እስከተደረጉ ድረስ አብዛኛው የራሺያ ግዛትና ህዝብ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ነገሮች ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ነበር። ለዚህም ነው እነ ሌኒን ይህንን ኋላ-ቀርነት በመገንዘብ በራሺያ ምድር ሁለ-ገብ የሆነ መብራት(Electrification) መግባት ወይም መስፋፋት እንዳለበትና፣ ይህም ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና ማደግ የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነ ያወጁት።

አሁንም ቢሆን ይህ ፖሊሲ በተለይም በእርሻው መስክ የተጠበቀውን ውጤት ባለማምጣቱ እነስታሊን በ1928 ዓ.ም በግዴታ ላይ የተመሰረተ የህብረት እርሻ ፕርግራም(Collectivization) በማስፋፋት በተለይም የከተማውን ህዝብ ለመመገብ ጥረት አደረጉ። በዚህ ዐይነቱ የግዳጅ የህብረት ፖሊሲ አማካይነት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቢሞትም፣  በተለይም ከ1930ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ሶቭየትህብረት በኢንዱስትሪ አብዮት የመረቃ ውጤት በማስገኘትና ከተማዎችን በመገንባት አነሰም በዛም ወደፊት ልትራመድ ችላለች። የምዕራቡ ዓለም የሶቭየትህብረትን ሁለ-ገብ ዕድገት ለመቀልበስ ሲል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰላዮችን በማሰማራቱ ይህ ሁኔታ በስታሊንና በተቀሩት የቦልሺቢኪ መሪዎች መሀከል መጠራጠርንና መጠላላትን አስከተለ። በተለይም እነ ቡሃሪን የመሳሰሉ የኢኮኖሚክስ ምሁራን ለቀቅ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመፈለጋቸውና ለዚህም በመከራክራቸው ስታሊን ይህንን ዐይነቱን አመለካከት አብዮቱን እንደመቀልበስ አድርጎ በመመልከቱ ቁጥራቸው የማይታወቁ ምሁራንን ጨረሰ።

ሶቭየትህብረት በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች መስኮች፣ ማለትም በባህልና በከተማዎች ግንባታ ወደፊት ልትገፋ የቻለችው የእነ ሂትለርን ጦር ድል ካደረገችና ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ፖሊሲ ማካሄድ ከጀመረች ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ በሶቭየትህብረትም ሆነ በተቀሩት ተቀጥያ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም የተካሄደው የግንባታ ፖሊሲ የኢኮኖሚክስ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከኋላ የመያዝ(Catching-Up Strategy) የኢንዱስትሪ ተከላ እንቅስቃሴ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ዐይነቱም ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ሰፊውን ህዝብ ያሳተፈ ሲሆን፣ ቀስ በቀስም ከድህነትና ከረሃብ እንዳላቀቀው የተረጋገጠ ነገር ነው። ስለሆነም በተለይም ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የሶሻሊስት አገሮች ሰፊው ህዝብ የመማር ዕድል ያገኘበት፣ የጤና መስክ የተስፋፋበት፣ ከተማዎች የተገነቡበትና ህዝቡም በንጹህ ቤት ውስጥ እንዲኖር የተደረገበት፣ የስራ መስክ የተረጋገጠበትና ህዝቡም ተከታታይ ገቢ እንዲያገኝ የተደረገበት ዘመን እንደነበር ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ የሁለ-ገብ ዕድገት እንቅስቃሴ ደግሞ በጊዜው የታሪክ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የመንግስት ቁጥጥር ያለበትና በዕቅድ ይካሄድ የነበረ በመሆኑ ለፈጠራ የሚያመች አልነበረም። ከዚህም በላይ አብዛኛዎቹ የሶሻሊስት አገሮች  ልክ እንደ ምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችና አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሬ-ሀብትን የሚቀራመቱ ወይም የሚበዘብዙ ስላልነበሩ ወደ ውስጥ ለዕድገት የሚያመቻቸውን የገንዘብም ሆነ የጥሬ-ሀብት እንደልብ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከሰባና ከሃምሳ ዐመት የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ግንባታ ሙከራ በኋላ ወደፊት ሊገፉ አልቻሉም።

በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሪክ ስንመረምር በአውሮፓ ምድር ውስጥም ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሊሆንና የበላይነትን ሊቀዳጅ የቻለው ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስና በስራ ላይ እንዲሰማራ በማድረግ ከብዙ ጊዜ የሙከራና የልምድ(Trial and Error) ግንባታ በኋላ እንደሆነ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የካፒታሊስት አገሮች በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው ሊያድጉ ወይም እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት የሚለው የተረት ወሬ ነው። ከዚህ በመነሳት በአ. አ እስከ ሚያዚያ 2018 ወር  ድረስ በህወሃት ግንባር ቀደምትነት ስልጣንን የያዘው የኢሃዴግን  አገዛዝ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካና የመንግስት ልማታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ውስጣዊ ይዘትና ተግባራዊነቱን እንመርምር።

 

የቀደመው አገዛዝ  አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንነት !

የቀድሞው የኢሃዴግ አገዛዝ ስልጣንን ከመንጠቁ በፊት እ.አ በ1974 ዓ.ም  የታሪክና የህብረተሰብ ግዴታ ሆኖ ደርግ ስልጣንን ከያዘ በኋላ የመሬት ላራሹ ታውጇል፤ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ተደርገዋል። እንደሚታወቀው አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት ከ500 000 በላይ የሚሆን ህዝብ በረሃብ ህይወቱን እንዳጣና፣ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነውም ህዝባችን ደግሞ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የተገደደ ነበር። አብዛኛው ህዝብ በጎጆ ቤት ውስጥ ሲኖር፣ ለብርድ፣ ለዝናብና ለአውሬ የተጋለጠ ነበር። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከ5% በታች የሆነውን ህዝብ የጠቀመ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተማዎች ጎልቶ ሲታይ፣ እዚያው በዚያው ደግሞ ድህነትና በሀብት መደለብ ተፋጠው የሚታዩበት ዘመን ነበር። በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተማዎች መሀከል ዘመናዊ ዕድገት የሚመስል ነገር ቢታይም፣ በጊዜው የነበረውን አጠቃላዩን የኢኮኖሚ አወቃቀር በምንመረምርበት ጊዜ በአገራችን ውስጥ ያልተስተካከለና ድህነትን የሚፈለፍል ኢኮኖሚ መሰል እንቅስቃሴ እዚህና እዚያ ይታይ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛው ተማሪ አስራሁለተኛን ክፍል ሲጨርስ የስራ ዕድል ለማግኘት ሲል ወደ አዲስአበባ የሚመጣ እንጂ እዚያው የተወለደበት፣ ያደገበትና የተማረበት ቦታ ስራ ማግኘት አይችልም ነበር። ሁለ-ገብ የሆነ የሙያ ማሰልጠኛ መማሪያ ትምህርትቤት በየክፍለ ሀገሩ ዋና ከተማዎችና አውራጃዎች ባለመኖሩ፣ በተለይም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የማይችለው አብዛኛው ወጣት ዝም ብሎ የሚንቀዋለል ነበር። ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የክፍለ-ሀገራት ከተማዎችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም የምክትል ወረዳዎች ኋላ-ቀር የሆኑ የአገዛዝ መዋቅሮች በመዘርጋታቸው፣ መስሪያቤቶቹ ባልተማሩ ሰዎች ይተዳደሩ የነበሩ ናቸው። በየክፍለ-ሀገራቱ የሚገኙት የአስተዳደር መስሪያቤቶች በየአካባቢው የሚገኘውን የሰውን ኃይልና የተፈጥሮን ሀብት ለማንቀሳቀስና ዕድገትን ለማምጣት የሚችሉ አልነበሩም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በየቦታው መተከል እንዳለባቸው የተገነዘቡ ባለመሆናቸው የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል በቀላሉ ይባክን ነበር። ስለሆነም በወቅቱ አብዮቱ መፈንዳቱ የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና ይህ አብዮት በአንድ በኩል በውስጣዊ የአደረጃጀት ድክመትና የሃሳብ አንድነትና (Lack of Unity of Thought) የርዕይ ጥራት አለመኖር፣ በሌላ ወገን ደግሞ አብዮቱን የሚቀናቀኑና ለውጥን የሚጠሉ የውስጥ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና በመተባበር ርብርቦሽ በማድረጋቸው የተፈለገው ለውጥ ሊመጣ አልቻለም። ትግሉ ዕድገትንና ለውጥን ለማምጣት የሚደረግ ከመሆን ይልቅ ስልጣንን ለመያዝ ከፍተኛ አትኩሮ ስለተሰጠው የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ርስበርስ መተላለቅ አመራ። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣትና ምሁራዊ ኃይል ህይወቱን እንዲያጣ ተደረገ።

ይህንን ዐይነቱን በቀላሉ ለመግለጽ የሚያስቸግረውን አብዮታዊ ሂደትና የዕድገት ሙከራ ነው የውጭና የውስጥ ኃይሎች ከሶሻሊዝም ጋር በማያያዝ ዘመቻ ማካሄድ የጀመሩት። ለውጡን የማይፈልጉ የውስጥ ኃይሎች በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በመደገፍ የአብዮቱን ውጤቶች ለመቀልበስና ስልጣንም የህዝብ እጅ ውስጥ እንዳይገባ ያላደረጉት ጥረት ይህ ነው አይባልም። ደርግ ከወደቀ በኋላ ስልጣንን የተረከበው አገዛዝ ዋናው ተግባሩም የአብዮቱን ድሎች አይ መቀልበስ ወይም በራሱ ስር በማጠቃለል ራሱን ማደለብ ነበር። የአብዮቱን ድሎች ለመቀልበስ ደግሞ የግዴታ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና  (IMF) በዓለም ባንክ(World Bank) የተጠናቀረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ ነበረበት። ደርግ ሲወድቅ ስልጣኑን የተረከበው አገዛዝ ከቀረቡለት ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ ይህንን የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በማቆላበጥ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እያለ የሚጠራውን ተግባራዊ ማድረግ ነበር። በፖሊሲው መሰረትም በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን ኢንዱስትሪዎች፣ ትላልቅ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ወደ ግል ሀብትነት መለወጥ ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን የህዝብ ሀብቶች ወደ ግል ሀብትነት ማዘዋወር እዚያው በዚያው የተካሄደና ጥቂት ግለሰቦች ገንዘብ ከባንክ በመበደር የተቀራመቱትና የገዙት ነው። ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው በጊዜው የነበረው ኢፈርት የሚባለው ትልቁ ኩባንያ ነው።

ከዚህ አልፎ በዚህ ዐይነቱ የፀረ-አብዮት ፖሊሲ እርምጃዎች አማካይነት  የአገራችን ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ እንዲል (Devaluation) ይደረጋል። የውጭው ንግድ ልቅ ይሆናል። ወደ ውስጥ ደግሞ በዋጋዎች ላይ ይደረግ የነበረው ቁጥጥር ይነሳል። በተጨማሪም ለማህበራዊ መስኮች ይመደብ የነበረው ባጀት ወደ ሌላ ይዛወራል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል ሲታወቅ፣ ዋና አላማውም የገበያን ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ  ነው የሚል ነበር።

ከ1980 ዓመታት ጀምሮ ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በብዙ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም በጋናና ናይጄሪያ ተግባራዊ ቢሆንም ወደ ውስጥ ሰፋ ያለና ግልጽ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ እንዲገነባ አላስቻለም። በእነዚህ አገሮችና በኢትዮጵያም ጭምር በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ተከላና ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል ሊካሄድና ሊዳብር አልቻለም። ከተማዎችና መንደሮችም በዕቅድ ሊሰሩና የተተከሉትም ኢንዱስትሪዎች ሰፋ ያለ የስራ መስክ ሊከፍቱና አስተማማኝ ገቢ ሊያስገቡ በፍጹም አልቻሉም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ በመተከል ለገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት መሰረት ሊጥሉ አልቻሉም። ይልቁንስ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአገልግሎት መስኩ መስፋፋት ነው በር የከፈተው። ስለሆነም ይህንን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ያደረጉ ኢትዮጵያና አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች  ገንዘባቸው ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ በመደረጉ፣ በአንድ በኩል ከውስጥ ግሽበትን ሲያስፋፋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የንግድ ሚዛናቸው ወደታች በማሽቆልቆል ችግር ውስጥ ገብተዋል። የንግድ ሚዛንን መዛባትና የባጀት ክፍተትን ለሟሟላት ደግሞ የግዴታ ከዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖች ብድር መጠየቅ ነበረባቸው። ኢትዮጵያና የተቀሩት የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች በሙሉ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመግባት በቀላሉ ሊፈቱ የማይችሉትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ማምረት ችለዋል። ይህም ማለት  በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ግፊት ተግባራዊ የሆነው የገበያ ኢኮኖሚ እነዚህን አገሮች ስርዓት ወዳለውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ወደ ተመሰረተ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ አወቃቀር እንዲያመሩ አላደረጋቸውም። በተከታታይ ተግባራዊ በሆነው ገንዘብን ዝቅ የማድረግ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ በተለይም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ $ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ሚዛን መዛባት ሲደርስበት፣ የውጭ ዕዳዋ ደግሞ ወደ $ 30 ቢሊዮን ወይም ከዚያ በላይ እንደሆነ ይታወቃል። የውጭው ዕዳው  አገሪቱ በዓመት ከምታመርተው ጠቅላላ ምርት $ 80.5 ቢሊዮን ውስጥ 38% የሚሆነውን ይይዛል። በሌላ አነጋገር፣ በተደጋጋሚ ተግባራዊ የሆነው የፀረ-አብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አገራችንን የባሰውኑ እያራቆታት ነው ማለት ነው። በዚያው መጠንም  የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሲሆን፣ በደሃና በሃብታም መሀከል ያለው ልዩነት እየሰፋ እንደመጣ መገንዘብ እንችላለን። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው አገዛዙ እስካሁን ድረስ ይከተል የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይንሳዊ ባህርይ ያለውና ችግርን ፈቺና አገርን መገንቢያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን፣ አገርን አውዳሚና ህብርተሰብን-የሚያዘበራርቀውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ማለት ነው።

ከዚህ ስንነሳ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ፍላጎቶችን ያሟላና ሊያሟላም የሚችል አይደለም። እንደትላንትናው ዛሬም ከ27 ዓመት በኋላ አብዛኛው ህዝባችን ንፁህ ውሃ የመጠጣትና የማግኘት ዕድል የለውም። በወዳደቁ ቤቶችና ጎጆ ቤቶች ውስጥ ነው የሚኖረው። ትምህርትቤቶች የፈራረሱ ናቸው። ህክምና እንደልብ አይገኝም። አብዛኛዎቹ ከተማዎችና መንደሮች የሰው ልጅ የሚኖርባቸው አይደሉም፤ አይመስሉምም። ሁሉም ከተማዎች በዕቅድ ከረጅም ጊዜ አንፃር ተብለው የታቀዱና የተገነቡ አይደሉም። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲው የሰውን ጤንነት ያቃወሰና የሰውም ኃይል አዲስ ዕውቀት በመገብየት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር መሰናክል የሆነ ነው። በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲውና ፖለቲካው አብዮታዊ ዲሞክራሲ  የሚያሰኘው ሳይሆን ፀረ-አብዮታዊና ፀረ-ዲሞክራሲ ነው። አብዮታዊነቱ ለጥቂት ሰዎች የመጣ ነው ማለት ይቻላል። ህዝባዊ ባህርይ የሌለውና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ያስቻለ አይደለም። ጥቂቶች በጉልበት የነጠቁትን ሀብትና የተቀዳጁትን ኃይል በመጠቀም ከፍተኛ ዘረፋ በማካሄድ ሊደልቡ የቻሉበት ሁኔታ ነው በጉልህ የሚታየው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ አብዮት ለጥቂቶች ብቻ የተካሄደ እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም። በጎሳ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የዚያው በዚያው የሀብት ሽግሽግና በሀብት መደለብ የተካሄደብትን ሁኔታ ነው  አብዮታዊ ዲሞክራሲ እየተባለ  በመጠራት ትልቅ ወንጀል የተሰራውና የተፈጸመው።

የኒዎ-ሊበራል የገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ 27 ዐመታት ሲጠጋው  በዚህ ዘመን በአገራችን ምድር ከፍተኛ የሆነ የባህል ውድመት ሊከሰትና የህብረተሰብአችንን እሴትና ባህል ሊበጣጥሰው ችሏል። ወጣት ሴት ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው  መሸት ሲል መንገድ ላይ በመቆም ለሴተኛ አዳሪነት እንዲጋለጡ ተደርገዋል። ቀደም ብሎ በትንሽ የሚታወቅ ወይንም ደግሞ ምንም ነገር የማይሰማ በወንዶች መሀከል የሚፈጸም የወሲብ ስራ በመስፋፋት የጠቅላላውን ህዝባችንን እሴት አናግቶታል። በተለይም በዕርዳታ ስም የገቡ የውጭ አገር ሰዎችና ለንግድ የሚመላለሱ አረቦች የአገራችንን ህዝብ ደሃ መሆን በመጠቀም ብልግና እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ሁሉ ይደረግ የነበረውና የሚደረገው በመንግስት ዕውቀት ነው። ስለሆነም ባለፉት 27 ዓመታት የአባለ-ዘር በሽታና የኤይድስ ቫይረስ በመስፋፋት ህዝባችንን አቅመ-ቢስና በሽተኛ አድርገውታል። ከዚህ በተጨማሪ የዕጽ ማጨስና የጨአት መቃም በመስፋፋታቸው ወጣቱ ትውልድ ሱሰኛ እንዲሆን ተደርጓል።  ገበያው በሊበራልዚም ስም ለውጭ ኃይሎች ክፍት በመሆኑ የውጭ ኃይሎች በወጣቱና በአገራችን ላይ የዕጽ ጦርነት(Opium War) ሊከፍቱ ችለዋል። የአገር እሴትና ባህል ሲፈራርስ ለመዋጋትና ለማጋለጥ የሚችል የሲቪል ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ባለመኖሩና፣ ተማርኩ የሚለውም ነገሩን ዝም ብሎ ስለሚመለከት አገራችንና ህዝባችን ወዴት አቅጣጫ እንደሚጓዙ የማያውቁበት ደራጃ ላይ ደርሰዋል። እንደሚታቀው ስለ አገር አንድነትና ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ይህንን አደገኛ የእሴት መበጣጠስ ከቁጥር ውስጥ በማስገባት የአገራችንን ሁኔታ ለመመርመር የማንችል ከሆነ ስለአገርና ባንዲራ ዝም ብለን ነው የምናወራው ማለት ነው። ሞራሉ የተከሰከስና በዕጽ ናላው እንዲዞር የተደረገ ወጣት ኃይል ሊያስብና ሊፈጥር ስለማይችል ይህንን ሁኔታ ዝም ብሎ ማየት የድርጊቱ ተባባሪ እንደመሆን ይቆጠራል። ከዚህ በተረፈ ወላጆች ሊረዷቸው  የማይችሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በየበረንዳው ተጥለውና ምግብ ከቆሻሻ መከማቻ ቦታ እየፈለጉ እንዲበሉ እንደተደረጉ እንመለከታለን። ከዚህም ባሻገር አጠቃላዩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር ያልታቀደ በመሆኑ አገራችን የቆሻሻ መከማቻ ልትሆን በቅታለች። ከአውሮፓና ከሌሎች አገሮች የሚመጡ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች፣ ያረጁ መኪናዎችና የፕላስቲክ ከረጢቶች በየቦታው ተበትነውና ተከማችተው በመገኘት ለጤንነት መቃወስ ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል። ስለሆነም ከዚህ ቀደም የማይታወቁ በሽታዎች  በአገራችን ምድር  በመስፋፋት በተለይም ወጣቱ ትውልድ የልዩ ልዩ ዐይነት በሽታዎች ሰለባ ሊሆን በቅቷል። ይህ ሁሉ ከላይ የተዘረዘረው ነገር የሆነውና የሚሆነው በመንግስት የሚደገፍ የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ተደርጓል በሚባልበት አገርና፣ የኢኮኖሚው ዕድገትም በ10%ና ከዚያ በላይ አድጓል በሚባልበት አገር ወስጥ ነው።

ይህንን ትተን ወደ ሌላ ጉዳይም ስንመጣም የአገራችን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ እናያለን። ባለፉት ሃያ ዐመታት በመንግስት ስር የሚተዳደር ቢሮ በመክፈት ወጣት ሴት ልጆቻችን ወደ አረብ አገሮች እንዲሸጡና ገረድ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ሰሞኑን የመንግስት ተወካዮች ይህንን የሴት ልጆችን ሽያጭ አስመልክቶ ከመንግስት ውጭ በጥቁር ገበያ በመሰማራት ወደ አረብ አገሮች የሚልኩ የተደራጁ ኃይሎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። የመንግስቱን ተወካዮች ገለፃ፤ለሰማ ይህንን ተግባር ሊፈጽም የሚችለው መንግስት ብቻ እንደሆነ አረጋግጠውልናል። የሚነሳስው ጥያቄ፣ ለመሆኑ በአገሪቱ ህገ-መንግስት ውስጥ መንግስት ከውጭ አገሮች ጋር በመስማማት ሴት ልጆችን ለመሸጥ ወይም ለመላክ የሚችል አንቀጽ አለ ወይ ? ቢኖርስ እንኳ አንድ ህዝብን እወክላለሁና አስተዳድራለሁ የሚል መንግስት ክውጭ መንግስታት ጋር በመስማማት ወጣት ሴት ልጆችን በግርድና የመላክ ተፈጥሮአዊ መብት አለው ወይ? ያም ሆነ ይህ ገንዘብ ለማኘትና ቤተሰብን ለመርዳት በሚል ሰበብ በታዳጊ ትውልድ ላይ እንደዚህ ዐይነት ወንጀል መፈጸም ከታሪክ ተጠያቂነት የሚያድን አይሆንም። ስለሆነም በአረብ አገሮች ተሰማርተው በግርድና የሚሰሩ ልጆቻችን ጥቂት የማይባሉት ህይወታቸውን እንዲያጡ ሲደረግ፣ ሌሎች ደግሞ በመደብድብ አካለ ስንኩላን ለመሆን በቅተዋል። የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ አለን የምንል ህዝብና በባንዲራችን የምንኮራ አንድ አገዛዝ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር እንደዚህ ዐይነቱን የመሰለ የታሪክ ወንጀል ሲፈጽም ዝም ብሎ ማየት አሁንም ቢሆን ከተጠያቂነት ሊያድነን በፍጹም አይችልም። ኢትዮጵያኖች ብቻ በመሆናችን ሳይሆን ነፃ ፈላጊና ለመብት ተቆርቋሪ እስከሆን ድረስ እንደዚህ ዐይነት ወንጀል ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከት በቀጥታ በአገራችን ላይ እንደመዝመት ይቆጠራል።

በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችን ምድር በመንግስት የሚደገፍ ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ሁለ-ገብ ልማት ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው  እየተባለ ባለማወቅ ዝም ብሎ የሚናፈሰው ፅንሰ-ሃሳብ በተለይም ታዳጊውን ወጣት በማሳሳት ላይ ይገኛሉ። በአገራችን ምድር አብዮታዊ ዲሞክራሲና በመንግስት የሚደገፍ ልማት ሲካሄድ ታይቶ አይታወቅም። ይህንን ሁሉ ትተን  በአገዛዙ ዘንድ ያለውን የዲሞክራሲ ባህላዊ ውይይት ጉዳይ በምንመረምርበት ጊዜ በኢህአዴግ አገዛዝ ውስጥ የፖሊሲ ክርክር ሲካሄድ ሰምተን አናውቅም። በመሀከላቸውም የሀብት ዘረፋንና መደለብን አስመልክቶ ክርክርና ውይይት ተካሂዶ አያውቅም። ዕድገትም በዚህ መልክ ነው የሚገለጸው ? ብለው ጠይቀውና ተከራክረው በፍጹም አያውቁም። ከዐመት ዐመት የገንዘብ ቅነሳ ፖሊሲ በማካሄድና የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማስፋፋት አገሪቱን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከተዋታል። የአገራችንን ትላልቅ የእርሻ መሬቶች አበባና ሸንኮራ አገዳ እንዲተከልባቸው በማድረግ የካፒታሊስት አገሮችን የባሰ በሀብት ክምችት እንዲደልቡ እያገዙ ነው።  በአንፃሩ ግን ሶቭየትህብረት በሌኒንም ሆነ በስታሊን ጊዜ፣ እንደዚሁም በቻይና የአብዮት ወቅት በእነ ማኦሴቱንግና በዴንግ ሲያዎፒንግ መሀከል የኢኮኖሚ ፖሊሲንም አስመልክቶ የጦፈ ክርክር ይካሄድ ነበር። አብዮትን ያካሄዱና አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተግባራዊ ያደረጉ እነዚህ አገሮችና ሌሎች የምስራቅ አውሮፓ አገሮች የአገሮቻቸውን የእርሻ መሬቶች ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በፍጹም አለወጡም። ስለሆነም የድሮውን አገዛዝ የዲሞክራሲያዊ አብዮታዊ መንግስት እያልን ከመጥራት ይልቅ በምዕራቡ ዓለም የሚደገፍ ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ዕድገት አገዛዝ  እያልን ብንጠራው ለትግል የሚያመች ይሆናል። ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የማይስማማ ፅንሰ-ሃሳብ የምንጠቀምና የምናራግብ ከሆነ የችግሩን ምንጭ በሚገባ ልንረዳ አንችልም ማለት ነው። ዋናውን ችግር ካልተረዳን ደግሞ ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማቅረብ አንችልም።  ስለሆነም ስለአንድ ህብረተሰብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ በምናወራበት ጊዜ መሰረታዊ ችግሩን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ይህንንም በቲዎሪ በሚገባ መተንተን አለብን፤ ምክንያቱም ካለቲዎሪ ድርጊት ወይም ተግባር ሊኖር አይችልምና።

የልማታዊ መንግስት ይዘት !

በኢኮኖሚክስ ሊትሬቸር ውስጥ ልማታዊ መንግስት(Developmental State) በመባል የሚታወቁት ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖርና ታይዋን ናቸው። ይህ ዐይነቱ የልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማው በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያን ማስፋፋት ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር ለውጭ ከረንሲ ማግኚያ በማለት ስትራቴጂክ በሆኑ መዋዕለ-ነዋዮች ላይ መረባረብ ነበር። በተለይም የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ አገዛዞች በመንግስት፣ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎችና  በባንኮች መሀከል መደጋገፍ እንዲኖር በማድረግ፣ ከውስጥ የኢኮኖሚውን ዕድገት በማፋጠን ቀስ በቀስ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ፣ በመኪናና በብረታ ብረት ምርቶች መንጠቀው በመሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነትና ከጥገኝነት በመላቀቅ ወደ ውጭ ደግሞ ሊከበሩ በቅተዋል። የመንግስትም ሚና ጥቂት ሰዎችን ማደለብ ሳይሆን ከውስጥ የተሰተካከለ ዕድገትን በማምጣት ኢኮኖሚው ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረግና በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው። ስለሆነም ለዚህ ዐይነቱ  በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ ዕድገት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቁልፍ ቦታ ሲኖራቸው፣   የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ደግሞ ሁለ-ገብ በሆነ ልዩ ዕውቀት የተደገፈ ነው።

በእነዚህ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆነው በመንግስት የተደገፈ የልማት ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚቃወምና፣ መንግስታቱም አንድም ጊዜ ይህንን ዐይነቱን ሀብት አውዳሚና በዕዳ ተብታቢ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ  ሲያደርጉ አልታየም። በተጨማሪም የውጭ ንግዳቸውን በመቆጣጠር ኢንዱስትሪዎቻቸው እንዲያድጉ የዕገዳ ፖሊሲ(Protectionism) ያካሂዱ ነበር፤ አሁንም ያካሂዳሉ። በተለይም ጃፓን የእርሻ መስኳን በከፍተኛ ደረጃ ትከላከላለች። እንደዚህ ዐይነቱ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በ17ኛው ፣ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካንም ጭምር በሌላ መልክ ተካሂዷል። የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ፖሊሲ ባያካሂዱ ኖሮ የኋላ ኋላ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለው መዳበር ባልቻለ ነበር። በታሪክ ውስጥ መንግስት ጣልቃ ሳይገባበት በግለሰብ ተሳትፎ ብቻ ያደገ የካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚ የለም። የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ጎልቶ የወጣበት ዘመን ሲሆን፣ እንደ ጀርመን የመሳሰሉት በጦርነቱ ከ80% በላይ የሚሆነው ኢኮኖሚያቸውና ከተማዎቻቸው የወደሙባቸው አገሮች በመንግስት በተደገፈ ፖሊሲና በልዩ የብድር ሲስተም (Credit System) በመመካት ነው በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከተማዎችን እንደገና መገንባት የቻሉት፤ ኢንዱስትሪዎቻቸውንም በመጠጋገን ሰፊ የስራ መስክ መክፈት የቻሉት። በዚህ መሰረት ቀስ በቀስ በሁሉም አቅጣጫ የውስጥ ገበያን ሲያስፋፉ፣ በሁሉም የፌዴራል ግዛቶች ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት ሊስፋፋና ሊዳብር ቻለ። በተለይም ትላልቅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ጣቢያዎች በመንግስት የሚደጎሙ ሲሆኑ፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችም ለቴክኖሎጂ ምርምር የበኩላቸውን ገንዘብ ይመድባሉ። ስለሆነም ልማታዊ የመንግስት ፖሊሲ በተለያዩ አገሮች በተለያየ መልክ የተካሄደና የሚካሄድም ነው። በተለይም ወደ ኋላ በቀሩ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገሮች በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ ፖሊሲ ማካሄዱ ኢኮኖሚዊና ታሪካዊ ግዴታ ነው። ይህ ካልሆነ አገራችን የማደግ ዕድሏ የመነመነ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገርና ህብረተሰብ የመኖር ዕድሏም እየተበላሸ ይሄዳል። ይህ በራሱ ደግሞ ማህበራዊ ውዝግብንና የእርስ በርስ ጦርነትን ያስከትላል። ስለሆነም ሰፋ ያለ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ አማራጭ የሌለው ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል።

ወደ አገራችን የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ ስንመጣ ላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው። ለዘረፋ የሚያመችና ጥቂቶችን የሚያደልብ ነው። ከጥገኝነትና ከለማኝነት የሚያላቅቅ አይደለም። ያልተስተካከለ ዕድገትና ዝርክርክነት ስር እንዲሰዱ ያደረገና የሚያደርግ ነው። ሰፋ ያለ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የስራ-ክፍፍል እንዳይዳብር ያደረገና የሚያደርግ ነው። በኢንዱስትሪዎች መሀከል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪዎችና በተቀሩት የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል መተሳሰር( Linkages or Value-added chain) እንዳይኖር ያደረገና የሚያደርግ ነው።  ስለሆነም ስራ ለሚፈልገው ሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት ያልቻለና የሚችልም አይደለም። ይህ ዐይነቱ ልማታዊ የመንግስት ፖሊሲ እንደሰሊጥ፣ ኑግ፣ ተልባና ሌሎችም የዘይት ጥራጥሬዎች በአገር ውስጥ እየተጨመቁና እየታሸጉ ለህዝቡ እንዲዳረሱ የሚያደርግ አይደለም። በተቃራኒው ግን  እነዚህ የዘይት ቅባት እህሎች በጥሬ መልካቸው ወደውጭ በመላክ ሀብት እንዲወድም  ሊደረግ በቅቷል። በዚያው መጠንም አገዛዙ ከውጭ አገር ጤንነት የሚያቃውስ ዘይት እያመጣ በመሸጥ የውጭው ንግድ ሚዛን እንዲዛባ አድርጓል ። ይህንን ዘርፍና እጣንን፣ እንዲሁም ቡናና ሻይን ጥቂቶች ባለሀብታሞች የሚቆጣጠሯቸው ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ ይህንን ዐይነቱን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ እያሉ መጥራት አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ወንጀልም እንደመስራት ይቆጠራል። ከዛሬ  ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቆሜያለሁ፣ ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ሁሉ ይህንን  ዐይነቱን አገር ጎጂና ህዝብን የማይጠቅም ፖሊሲ ልማታዊ እያለ መጥራት አይገባውም። ከዚህ ስህተት መቆጠብ አለብን። ዝምብለን ሳናውቅ የምናራግበው መፈክር ግልጽ ለሆነ ፖሊሲ የሚያመች አይደለም። ወደፊት ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነና ድህነትንና ረሃብን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የሚያወድም ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያግድ ነው። በዚህ ላይ መስማማት ካለ ኢኮኖሚክስ የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ በመጠኑም ቢሆን ላብራራ። ስለኢኮኖሚክስ ምንነት ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው ስለኢኮኖሚ ዕድገት ወይም ስለልማት ማውራት የሚቻለው።

ኢኮኖሚክስ ማለት ምን ማለት ነው ?

በአገራችን የተልምዶ አጠራር ኢኮኖሚክስ ማለት የምጣኔ ሀብት ትምህርት እየተባለ ነው የሚጠራው። የታወቀው የግሪክ ፈላስፋ አርስቲቶለስ ደግሞ ኢኮኖሚክስ ማለት የቤተሰብ ማስተዳደሪያ( Household Management) እያለ ይጠራዋል። በአገራችን የተለመደው አጠራር ስለኢኮኖሚክስ የተሟላ ነገር ሊነግረን በፍጹም አይችልም። በሌላ ወገን ግን አርስቲቶለስ ኢኮኖሚክስን የቤተሰብ ማስተዳደሪያ ዘዴ ነው ብሎ ቢጠራው የሚያስገርም አይደለም። በጊዜው የግሪክ ህዝብ በተለይም በከተማዎች ውስጥ ይኖር የነበረው እንደዛሬው ሰፋ ባለመልክ የሚገለጽ የህብረተሰብ አወቃቀር አልነበረውም። አብዛኛው የኢኮኖሚ ክንዋኔ በትናንሽ መስክ የሚካሄድ ስለነበር ሰፋ ያለ የገበያ ኢኮኖሚ የዳበረበት ዘመን አልነበረም። ይሁንና አርስቲቶለስም ሆነ ፕላቶ ስለንግድ ልውውጥ፣ ስለስራ-ክፍፍልና ስለገንዘብ ምንነትና አስፈላጊነት በሰፊው አትተዋል። የእነዚህንንም ትርጉምና በአንድ አገር ውስጥም ሰለሚኖራቸው የዕድገት ሚናና ለህብረተሰብ መተሳሰር አስፈላጊ እንደሆኑ በሚገባ አብራርተዋል።

አገሮች ቀስ በቀስ ወደ ህብረ-ብሄር ሲሸጋገሩና ማዕከላዊ መንግስታት ሲቋቋሙ ይታወቅ የነበረው ኢኮኖሚክስ ሳይሆን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመባል ነው። ይህም ማለት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘና የአንድን ህዝብ ዕድል መወሰኛ ዘዴ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ስለኢኮኖሚክስ ሲወራ ስለብሄራዊ ኢኮኖሚ ማውራት እንጂ በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል የሚገለጽ አልነበረም። በተለይም በጀርመን ምድር በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንደ አሜሪካንና እንግሊዝ ኢኮኖሚክስ እየተባለ የሚጠራ ሳይሆን ብሄራዊ ኢኮኖሚ(National Economy) እየተባለ ነው። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በጀርመን ምድር ፍልስፍናና የህብረተሰብ ሳይንስ በሰፊው በመስፋፋታቸው በጊዜው የተነሱት ምሁራን ኢኮኖሚን ከማህበራዊና ከብሄራዊ ባህርይው ነጥለው አያዩትም ነበር። በእነሱም ዕምነት የኢኮኖሚ ዕድገት የማህበራዊ ጥያቄዎችንም(The Social Question) የሚያካትትና የሚፈታ መሆን አለበት። እነ አዳም ስሚዝም ቢሆኑ ስለ ስራ-ክፍፍል አስፈላጊነት፣ ስለማሺነሪና ሰለሰፊ ገበያ በማተት ኢኮኖሚ  ብሄራዊ ባህርይ እንዳለው ለየት ባለመልክ ሊገልጹ ችለዋል። በመሀከላቸው ያለው ልዩነት ግን ነፃ ንግድ በሚለውና ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት የለበትም ወይም አለበት በሚለው ላይ ነው። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት የጀርመን ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት ይመለከቱ የነበረው በተናጠል ሳይሆን ሁለንታዊ በሆነ መልክ ስለነበር እንደዚህ ዐይነት የመንግስትን ሚና አጉልቶ የሚያሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የህብረተሰብ ግንባታ አካሄድ ቅድሚያ መስጠታቸውና መሆንም እንዳለበት ማመልከታቸውና ማስተማራቸው የሚገርም አይደለም።

የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳብ እየተኮላሸ የመጣው የኒዎ-ክላሲካልስ ወይም የኒዎ-ሊበራል ምሁሮች ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ፅንሰ-ሃሳቡን እያዛነፉ በመምጣታቸው ነው። በእነሱ ዕምነትም፣ የተመጠነ ሀብት ተግባራዊ የሚሆንበት(The Allocation of Scarce Resources)፣ የአቅራቢና የጠያቂ ጉዳይ(Supply and Demand) የፍጆታ ጉዳይ፣ አንድን ተመጥኖ የሚገኝ ሀብት አማራጭ በሆኑ ወይም በሚያዋጣ ነገር ላይ ማዋል፣ የመሳሰሉትን በማስፋፋትና የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ሊትሬቸሮችን በማጣበብ ከሳይንሳዊ ባህርይው ተነጥሎ እንዲታይ አድርገውታል። ስለሆነም ኢኮኖሚክስና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በማሰብ ኃይልና አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ የሚዳብር ሳይሆን፣ ከላይ በተገለጹት መልኮች ብቻ ነው። ከዚህም በላይ ይህ ዐይነት የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳብ ስለኢንስቲቱሽን አስፈላጊነትና ስለፈጠራ(Innovation)፣ እንዲሁም ስለህብረተሰባዊ አደረጃጀት በፍጹም አያወራም። ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በግለሰቦች መሀከል የሚካሄድ(Methodological Individualism) ሲሆን፣ ህብረተሰብአዊ ባህርይ የለውም። አንድ አገር የየግለሰቦች ድምር ውጤት እንጂ፣ እንደማህበረሰብና ህብረተሰብ የሚታይ አይደለም። እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ዓለምና ለራሱ ብቻ የሚኖር ነው።  በተለይም ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ በማቲማቲክስ እያሸበረቀ በመምጣቱ፣ አንዳንድ የኢኮኖሚክስ ምሁራንና እንደ ሚሮቭስኪ የመሳሰሉት የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ይህ ዐይነቱን አካሄድ የማቲማቲክስን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረት እንጂ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ሊፈታ እንደማይችል አረጋግጠዋል። ሰልሆነም በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ምሁሮች ዕምነት ኢኮኖሚክስ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲህም ከምርት ክንዋኔ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን፣ በንጹህ መልኩ ከንግድና ከፍጆታ ጋር ብቻ የሚያያዝ ነው። በንጹህ መልኩም የአንድን ሰው በፍጆታ መርካትንና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በምርት ክንውን ውስጥ የሚሳተፈው ባለሀብት ትርፍን ለማትረፍ የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ ነው።  ይህ ዐይነቱ አገላለጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደቫይረስ በመስፋፋቱ በተለይም በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ድህነትና መዝረክረክ የሚስፋፋበት መሳሪያ ሊሆን በቅቷል። በየአገሮቹ ውስጥ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት እያለ ይህንን በማውጣትና በመለወጥ ወይም በማምረት ለመጠቀም ያልተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይም ዶላርና ኦይሮ የዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥና የሀብት ማከማቻ መሳሪያዎች(Exchange and Reserve Currency) ናቸው ተብሎ ተቀባይነት በማግኘታቸው ብዙ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ካለዶላርና ካለኦይሮ ማሳደግ የማይችሉ እየመሰላቸው የባሰ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመግባት ህዝቦቻቸውን እያደኸዩና ኋላ-ቀርነት ስር እንዲሰድ እያደረጉ ነው። በሌላ ወገን ግን ስልጣኔዎች በሙሉ ሊስፋፏና ሊዳብሩ የቻሉት ካለዶላርና ካለኦይሮ ነው። የግብጽ፣ የግሪክ፣ የሮማውያንና የቻይና ስልጣኔዎች በሙሉ ዕውን የሆኑት በሰው የማሰብ ኃይልና ስራ ብቻ ነው። በመሆኑም በታላላቅ ፈላስፋዎችና ኢኮኖሚስቶች ምርምር መሰረት ማለትም በፊዞክራቶች፣ በመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ምሁራን፣ በክላሲካል ኢኮኖሚስቶችና በካርል ማርክስም ጭምር የሰው ልጅ ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ናቸው ዋናው የሀብት ወይም የዕድገት ምንጮች። ገንዘብ ይህንን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚውል መሳሪያ ብቻ ነው። ገንዘብም ራሱ የሰራ-ክፍፍልና የገበያ ዕድገት መዳበር ውጤት እንጂ በራሱ ለዕድገት ቅድመ-ሁኔታ አይደለም።

ወደ ዋናው መሰረተ-ሃስብ ስንመጣ ኢኮኖሚክስ ማለት ሌላ ነገር ሳይሆን አንድን ነገር በሰው ጉልበት፣ በማሽንና በኃይል(Energy) አማካይነት መለወጥ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም የጥሬ ሀብት ጠቀሜታ ላይ ከመዋሉ በፊት ካለበት ሁኔታ ወደ ሌላ ነገር መለወጥ አለበት። ለምሳሌ ብረትን ከማግኘታችን በፊት በእሳትና በማሽን አማካይነት ማቅለጥ አለብን። እንዲሁም በማሽን አማካይነት የተለያየ ቅርጽ በመስጠት የምርት መሳሪያዎችን ለመስራት እንችላለን። ሌሎች የጥሬ-ሀብትና እህሎችም በዚህ ዐይነት የክንውን ዘዴ ነው ለጠቀሜታ የሚውሉት። ሌላ ምስጢር የላቸውም። ይህም ማለት ኢኮኖሚክስ ካለሳይንሳዊ ምርምር፣ ካለቴክኖሎጂና ካለምርት ክንዋኔ ሊታሰብ በፍጹም አይችልም። ኢኮኖሚክስም ከጠቅላላው ከአንድ አገር ዕድገት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የአንድ አገር ጥንካሬና ድክመት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ በሚካሄድና፣ ሳይንሰ-አልባ በሆነ መልክ በሚገለጽ ተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚክስ አማካይነት ነው። በሌላ አነጋገር ኢኮኖሚክስን ከፖለቲካ፣ ከማህበረሰብ፣ ከባህል፣ ከሳይንስ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከማኑፋክቱርና ከማሽን ነጥሎ ማየት እጅግ አደገኛ ነው። አንድ አገር በባህል ልትበለጽግ የምትችለውና ውብ ውብ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት የምትችለው ኢኮኖሚክስ በሁለመንታዊ ጎኑ ከታየ ብቻ ነው። ስለሆነም የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ፖሊሲዎች በሙሉ ይህንን ዐይነቱን ሁለ-ገብ የሆነ የአገር ግንባታ ዘዴ የሚጻረሩ ናቸው ። ስለዚህ ነው በአገራችን ምድር ባለፉት ስድሳ ዐመታት ድህነትና ረሃብ እየተስፋፉ የመጡት። በዚህ ዐይነቱ አካሄድ ነው ዕውነተኛ ብሄራዊ ሀብት መፍጠርና አገርን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ መገንባት ያልተቻለው።  የአገርንም የሰውን ጉልበትና የጥሬሀብቶችን በስርዓት መጠቀም ያልተቻለው አገዛዞቻችን የተሳሳተ የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ በመከተላቸው ነው። ከዚህ ስንነሳ አገራችንን በፀና መሰረት ላይ መገንባት ከፈለግናና ለተከታታዩም ትውልድ የሚመካበት ነገር ጥለን ለመሄድ ከፈለግን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክና በአጠቃላይ ሲታይ ከዓለም ኮሙኒቲው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ መላቀቅ አለብን። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ አሁን ያለውንና አፍጦ አግጦ የሚታየውን ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም የስራ-አጥነት፣ የከተማዎች በስርዓት አለመገንባትና ሀብትም ወደ አንድ አቅጣጫ መፍሰስ ስንመለከት የእርስዎ አገዛዝ ደረጃ በደረጃ መውሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ። እንዚህን በቅደም ተከተል እንመልከት።

 

ኢኮኖሚክስና የኢኮኖሚ ፖሊሲ መፍታት ያለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች !

በመጀመሪያ ደረጃ በአውሮፓ ህብረተሰብ የግንባታ ታሪክ ውስጥ ቅድሚያ የተሰጣቸው እንደምግብና መጠለያ እንዲሁም ንጹህ ውሃ የመሳሰሉትን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ማሟላት ነው። በተለይም የምግብን ችግር ለመቅረፍ በእርሻው መስክ ሳይንሳዊ ጥናት በማካሄድና ለምርታማነት የሚያገለግሉ የምርት መሳሪያዎችንና ማዳበሪያዎችን በማቅረብ ቀስ በቀስ የምግብ ችግርን መቅረፍ ተቀዳሚው ተግባር ነበር። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ሊሰራና የበለጠ ምርታማ ሊሆን የሚችለው አስፈላጊውን የምግብ ዐይነቶች ሲያገኝ ብቻ ነው። ይህንን መሰረታዊ ነገር ሳንፈታና፣ በተጨማሪም ገጠሩን የመኖሪያና የመዝናኛ ቦታ ለማድረግ ስነ-ስርዓት ያለው የልማት ስራ ማካሄድ ካልቻልን የአገራችን የረጅም ጊዜ ችግር ወደፊትም ይቀጥላል። እንደሚታወቀው ገበሬው ነው በስንት ልፋት በጠዋት እየተነሳና ረጅም ጉዞ በመጓዝና በመድከም አርሶ አፍርቶ የከተማውን ህዝብ የሚመግበው። የሰው ልጅ ባህርይ ሆኖ ከተማ ውስጥ የሚኖር ወይም በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ አንድን ህዝብ ለመመገብ ገበሬው የቱን ያህል እንደሚደክም ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት ነው። በዚህም የተነሳ እርሻና የገበሬው ልፋት እንዳልባሌ በመታየታቸው በዚህ መስክ መደረግ ያለበት ርብርቦሽ በጣም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለሆነም ገጠሩን፣ የእርሻ ምርት መለገሻ፣ ለማገዶና ለልዩ ልዩ ቁሳቁሶች የሚውሉ ዛፎችን ማብቀያ፣ የአውሬዎችና የልዩ ልዩ ወፎችና እንሴክቶች መኖሪያና፣ የንጹህ አየር መተንፈሻ መሆኑን ተገንዝቦ በተለይም የእርሻ ሚኒስተር አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ መንግስትዎ እንዲከታተል አጥብቄ አሳስባለሁ። በዚህ አጋጣሚም በተለይም የደን ልማት መካሄድ ያለበትና ዛፎችም ካለጥናት እንዳይቆረጡ የእርሻ ሚኒስተር አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት። ለማገዶ፣ ለሳንቃና ለቤት ስራ፣ እንዲሁም አካባቢውን ለመጠበቅ የሚያገለግሉ ዛፎች ተለያይተው በአንድ አካባቢ ቢተከሉና እንክብካቤ ቢደረግላቸው ሚዛናዊ ስራ መስራት ይቻላል። ሰፊው የገጠር ህዝብ ለማሞቂያ ወይም ለመቀቀያ ሲል ዛፍን ስለሚቆርጥ በላፉት 27 ዓመታት የዛፍ ውድመት ተስፋፍቷል። ይህንን በሚመለከት የርስዎ መንግስት ልዩ የደን ጥበቃና ልማት ህግ እንደሚያወጣ ተስፋ አደርጋለሁ።

በሁለተኛ ደረጃ የንጹህ ውሃ ማግኘትን ጉዳይ ነው። ይህን ጉዳይ በሚመለከት ልክ እንደምግብ ተከታታይ የኢትዮጵያ አገዛዞች አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት አልቻሉም። ስለሆነም ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ንጹህ ውሃ የማግኘት ዕድል የለውም። በተለይም የገጠሩ ህዝብ ብዙ ርቀት ያለው መንገድ በመጓዝ ነው ከወንዝ ውሃ እየቀዳ ተሸክሞ የሚያመጣው።  አሁንም የገጠሩ ህዝብ እንደማዕከለኛው ዘመን የሚኖር ነው የሚመስለው። የንጹህ ውሃ ማግኘትን ጉዳይ በሚመለከት ወደ ከተሞችና መንደሮች ስንመጣም እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በየክልሉ ወረዳዎችና ምክትል ወረዳዎች ያሉ አስተዳዳሪዎች ብቃትነት ስለሌላቸው ይህንን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም።  በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ ውስጥም የንጹህ ውሃ ማግኘት ችግር አፍጦ አግጦ የሚታይ ነው። ባለፉት 27 ዓመታት በአዲስ አበባ ውስጥ ካለዕቅድ ብዙ ሁቴል ቤቶችና ትላልቅ ህንጻዎች በመሰራታቸው ውሃንና መብራትን በከፍተኛ ደረጃ እየተጋሩና ሰፊው ህዝብ በንጹህ ውሃ እጦትና በመብራት መቆራረጥ እንዲቸገር ተደርጓል። ስለሆነም ማንኛችንም ንጹህ ውሃ ሳንጠጣ አንድም ቀን ማደር እንደማንችል ተገንዝበን ሰፊው ህዝብ ንጹህ ውሃ ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔታ መጠናት፣ መታቀድና ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ስለልማት ሲወራ በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ ከመሳሰሉት መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች መነሳት ያስፈልጋል።

በሶስተኛ ደረጃ መፈታት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። እንደምናየው ህዝባችን አሁንም ቢሆን እንደማዕከለኛው ዘመን የሚኖር ነው። በአገራችን ውስጥ ሰብአዊነትን የተላበሰ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ  ለሰው ልጅ ያለን አመለካከት እጅግ የተዛባ ነው። ደካማውንና ደሃውን እንደሰው አለማየትና፣ ፍላጎትና ምኞት እንደሌለው  ሰው አድርጎ መቁጠር በአገራችን የተለመደ ነው። ይህ ዐይነቱ ችግር በአገራችን ብቻ ያለ ሳይሆን በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተንሰራፋና ሰፊውን ህዝብ እንደሰው የማይታይበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንደሚታወቀው አንድ ህዝብ አገሩን አገሬ ብሎ የሚጠራው መኖር ሲችል ብቻ ነው። የሰው ልጅም መሰረታዊ ነፃነት የሚለካው በአኗኗሩ ነው። ከዚህ ስንነሳ የህዝባችንን የአኗኗር ዘዴ ለመለወጥ የግዴታ ሁለንታዊ በሆነ መልክ መወሰድ የሚገባቸው ነገሮች አሉ።  በተለይም በከተማ አገነባብ ዕቅድና በአርክቴክቸር የሰለጠኑ ሙያተኞች ከሶስዮሎጂስቶች፣ ከፈላስፋዎችና ከህሊና-ሳይንስ ተመራማሪዎች ጋር በመመካከር ህዝባዊ ባህርይ ያላቸውና ዘላቂነት የሚኖራቸው የቤት አሰራሮች በአገራችን ምድር መለመድ አለባቸው። ከተማዎች በደንብ ከታቀዱና ሰውም መኖሪያ ካገኘ አንዳንዱ ከአመጽ ይቆጠባል። እንደሚታወቀው ማንም ሰው አመጸኛ ሆኖ አይወለድም። በአንድ አገር ውስጥ ብዙም ሳይታሰቡ ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮች ዲሲፕሊንነት እንዳይኖር ያደርጋሉ። በስርዓት ያልታቀደና ግልጽ የአሰራር ስልትን ያለመደ ማህበረሰብ  ጤናማና ኃላፊነት የሚሰማውን ዜጋ ማፍራት አይችልም።

በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩ ትላልቅ ህንፃዎች ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም። በአርቆ አስተዋይነትና በጥበብ የተሰሩ አይደሉም። በተለይም የኮዴምንዩም የቤት አሰራሮች ለጌቶ(Ghetto) የሚያመቹ ናቸው። አመጽንና ብልሹ ባህልን ሊያስፋፉ የሚችሉ ናቸው። የቤቶቹ አሰራሮች ከአገራችን ባህል ጋር የሚጓዙ አይደሉም። በተለይም ሽማግሌዎችንና አሮጊቶችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተሰሩ አይደሉም። ወደ ውስጥ የደረጃዎቹ መወጣጫዎች መሰረታዊ ህግን የጠበቁ አይደሉም። ሰውን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ናቸው። ከዚህም በላይ ቤቶቹ ጓሮ የላቸውም። የልጆች መጫወቻዎችም አንድ ላይ አልተሰሩም። በተለይም ብዙ ህዝብ በአንድ አካባቢ እንዲኖር ሲደረግ የግዴታ አብረው መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። በአካባቢው የቆሻሻ መጣያና ሌሎች ለአካባቢው ንጽህና የሚያስፈልጉ ጉዳዮች በሙሉ ታስበው መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። እንደሚታወቀው ማንም ሰው በዚህች ዓለም ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚኖረው። ሲኖር ደግሞ ደስታን ይፈልጋል። እንደየአሰራራቸው መኖሪያ ቤቶችና አካባቢዎች የደስታ መግለጫዎች ናቸው።  ወደ ሌሎች ትላልቅ ህንጻዎች ስንመጣ እንደዚሁ አስቸጋሪ ሁኔታ እናያለን። አብዛኛዎች ከአራት ፎቅ በላይ ያላቸው ህንጻዎች የግዴታ መወጣጫ ሊፍት ያስፈልጋቸዋል። በየህንጻዎች ውስጥ ይህንን ማስገባት ብዙ ወጪን መጠየቁ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪንንም ይጋራል። ሲበላሹም ጠጋኝ ያስፈልጋል። በዚህ ሙያ የሰለጠነ ሰው ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በላይ ሊፍቶች በመብራት የሚንቀሳቀሱ ስለሆነ የግዴታ መብራትን ይጋራሉ። ያም ተባለ ይህ የመኖሪያ ቤቶችም ሆነ የንግድና የመንግስት መስሪያቤቶች ከአገሪቱ የሀብት ሁኔታ፣ ከባህልና ከታሪክ ጋር እየተመዛዘኑ ቢገነቡ ይሻላል። ከዚህም ባሻገር ዘላቂነት ያላቸውና ለማደስም የሚያስቸግሩ መሆን የለባቸውም። የዘላቂነታቸው ጉዳይ ደግሞ በማቴሪያሉ ዐይነት የሚወሰን ነው። የቤት አሰራሮች ከብሎኬት ይልቅ በጡብና በዲንጋይ ቢሰሩ ጤናማና ለአገራችን አየር የሚስማሙና እንደ አየሩ ሁኔታ ራሳቸውን የሚያቀናጁ ናቸው።

በአራተኛ ደረጃ መፈታት ያለበት ጉዳይ አጠቃላዩን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመለከት ነው። ያለፉትን ስድሳ ዐመታት የአገራችንን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ስንመለከት ከህዝብና ከአገር ግንባታ ጋር ተያይዘው የታቀዱ ባለመሆናቸው በአገራችን ምድር በተለያየ መልክ ለተገለጹትና ለሚገለጹት ውስብስብ ችግሮች እንደዋና ምክንያቶች ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ ናቸውም። የብሄረሰብ ችግርና በየቦታው የሚታየው የአመጽ ሁኔታ ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ማንኛውም ሰው የሚሰራ ከሆነና  አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ካለው ቤተሰብ መስርቶ ልጆት ወልዶ ደስታን መጎናጸፍ ይመኛል። ሁሉም ሰው በስራ ከተወጠረና የሚሯሯጥ ከሆነ ሌላ መጥፎ ነገር አይታየውም። ስለሆነም ለአንድ አገር ሰላም መስፈን የግዴታ የኢኮኖሚ ጉዳይ መፈታት አለበት።

እንደሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም በአገራችን ያለው ችግር የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) የሚባለው መሰረታዊ ጉዳይ አለመታወቁ ነው። ስለሆነም መንግስታት የሚያተኩሩት የውጭ ከረንሲ ለማግኘት ሲሉ ለውጭ ገበያ ላይ በሚቀርቡ የጥሬ-ሀብቶችና የእርሻ ሰብሎች ላይ መሰመራት ነው። ይህንንም የሚያደርጉት በውጭ አገር ኤክስፐርቶች እየተመከሩ ነው። ስለሆነም የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ(Inward-looking strategey) የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተሉ ለተስተካከለና ፍትሃዊነት ለሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ይጠቅማል። ይህንንም በሚመለከት በተለይም እንደ ቻምበርስ ኦፍ ኮመርስና የኢንቬስትሜንት ቢሮ ምን ምን ዐይነት ኢንዱስትሪዎች በየቦታው ቢቋቋሙ ሰፋ ያለ ብሄራዊ ሀብት መፍጠር ይቻላል? ብለው ምርምርና በቂ ጥናት ማድረግ አለባቸው።

በአገራችን ያለው ሌላው ችግር ሀብት ወይም ገንዘብ ያለው ቴክኖሎጂ በሆኑ ነገሮች ላይ አለመሰማራቱ ነው። አብዛኛው በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ከመሰማራት ይልቅ ቶሎ ቶሎ ትርፍ ወደሚያገኝበትና ወደሚከብርበት ላይ ነው የሚሰማራው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በየቦታው ተስፋፍተው ይገኛሉ። ሁሉም ቡና አምራች መሆን ይፈልጋል። አንዱ ሆቴል ቤት ሲሰራ ሌላውም ሆቴል ቤት ልስራ ብሎ ይነሳል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ እንደባህል ሆኖ በመወሰዱ የአገር ውስጥ ሀብት በከንቱ ይወድማል። የስራ መስክ ለሚፈልገውም በየቦታው በቂ የስራ መስክ መክፈት አይቻልም።

ስለሆነም አንድ አገር ሊያድግና ሊያብብ የሚችለው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፍትሃዊነት የሚኖረው ሰፊው ህዝብና ሀብታሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ሲሰማሩ ነው። እንደ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችንና የቤት የፍጆታ ዕቃዎችንና ቁሳቁሶችን መስራትና ማምረት ኢኮኖሚውንም ሆነ ህብረተሰቡን የበለጠ እንዲተሳሰሩ ያደርጋቸዋል። በኢኮኖሚክስ ሳይንስ መተሳሰርና(Linkages) ተጨማሪ ምርት ማምረት(Value added) የሚባሉ መሰረተ-ሃሳቦች አሉ። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች በጭንቅላት ውስጥ ሲቋጠሩ ነው አንድን አገር በሁሉም አቅጣጫ መገንባት የሚቻለው። እንደምናየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሳይንስን ያልተከተሉና ፈራቸውን እየለቀቁ በመምጣታቸው በየአገሮች ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እየታየ ነው። ስግብግብነትና ስልጣንን መቀዳጀት እንደዋና ፈሊጥ እየታዩ በመምጣታቸው በየአገሮች ውስጥ ባህሎች እየፈራረሱ ነው። ባህላዊ መሳሪዎችንና ዕቃዎችን ከመስራት ይልቅ ሁሉም ነገር ከትርፍ አንፃር ስለሚተለም በየአገሩ ያሉ ህዝቦች ወዴት እንደሚጓዙ እንዳያውቁ ተደርገዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዎች በየአገሩ ያሉ መሪዎች ሲሆኑ፣ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ንቃተ-ህሊናቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው። ስለሆነም ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እንዲሁም የኢኮሎጂ ኃላፊነት አይደሉም። ህብረተሰብም ምን ማለት እንደሆነ የሚገባቸው አይደሉም።

ከዚህ በመነሳት በአገራችን ምድር በአንዳንድ ቦታዎች የሚቋቋሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብዙ ነገርችን ያላገናዘቡና ዘላቂነትም ያላቸው አይደሉም። እንደሚታወቀው በየኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱት የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችና ጫማዎች ለውጭ ገበያ ተብለው ነው። ይህም ማለት አንድን አገር በሁሉም አቅጣጫ በማሳደግ የሚጫወቱት ሚና አልቦ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር የውጭ ገበያው ከተለያዩ አገሮች በሚመረቱ ምርቶች የተያዘ እንደመሆኑ መጠን የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች በርካሽ የሚሸጡ ናቸው። ይህም ማለት የውጭ ምንዛሪን ችግር ለመቅረፍ አይቻልም ማለት ነው።

ከዚህ ዐይነቱ አካሄድ ይልቅ በማሺንና በማኑፋክቱር ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማቋቋሙ የተሻለ ነው። ይህንን በሚመለከት ከቻይና ይልቅ እንደ አውስትሪያ ከመሳሰሉት አገሮች ጋር ልዩ ስምምነት በማድረግ የቴክኖሎጂ ልውውጥ ማድረግ ይቻላል።

በአምስተኛ ደረጃ በአገራችን ምድር ዕድገትን ለማፋጠን ከተፈለገ ከዩኒቨርሲቲዎች ይልቅ ተግባራዊነት ያለው የተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት በየቦታው ቢከፈት ጥሩ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ አማራጭነት የሌለውና ለአንድ አገር ዕድገት ቁልፍና መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ይህንንም በሚመለከት ከአውስትሪያና ከጀርመን ጋር ልዩ ስምምነት ማድረግ ይቻላል። ዋናው ቁም ነገር ግን ፍላጎት መኖሩና ዕድገት የሚባለውን መሰረተሃሳብ መረዳት ነው።

በአገራችን ምድር ፍትሃዊነት ያለበትና ፈጣንና የተስተካከለ ዕድገት እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ መላቀቅ ይኖርብናል። ሁለ-ገብ የሆነ የአገር ግንባታ ፖሊሲ መከተሉ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ለዚህ ቁልፉ ደግሞ ሰፋ ያለ የማኑፋክቸር እንቅስቅሴ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ናቸው።

በስድስተኛ ደረጃ፣ የሚነሳው ጥያቄና መሰረተ-ሃሳብ ይህንን ሁሉ አጠቃላዩን የአገራችንን ኢኮኖሚና  የአገር ግንባታ  ገንዘብ ከየት በማምጣት ነው ለመደጎም ወይንም ፋይናንስ ለማድረግ የምንችለው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥና በአገር ግንባታ አካሄድ ማንኛውም አገር ከምንም በመነሳትና በማሰብ ኃይሉ በመመራት ነው ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ማድረግ የቻለውና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን አውጥቶ በመለወጥ ለጠቀሜታ ያዋለው። እንደዚሁም ገንዘብም የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ውጤት ሲሆን፣ ከስራ ክፍፍልና ከገበያ ማደግ ጋር የተያያዘ ነው። ፓውንድና ዶላር ወይም ኦይሮ የዓለም አቀፍ የንግድ መለዋወጫና የሃብትም ማጠራቀሚያ ገንዘቦች መሆን እስከቻሉ ድረስ እያንዳንዱ አገር በራሱ ገንዘብ ነው አገሩን ሊገነባ የቻለው። እንግሊዝ፣ ጀርመንና አሜሪካን በራሳቸው ገንዘብ ነው የኢንዱስትሪ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን የቻሉት። በካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊነት የተነሳ ሁሉ ነገር ተጣሞና ተዛብቶ ስለሚቀርብ በተለይም እንደኛ ያሉ አገሮች ካለዶላርና ኦይሮ ማደግ የማይቻል ይመስላቸዋል። ስለሆነም የብድር ወጥመድ ውስጥ በመግባት የማይወጡት ሁኔታው ውስጥ በመስመጥ በዕዳ ከፋይነት የአገራቸውን ሀብት እንዲያሰተላልፉ ተገደዋል። የዚህ ሁሉ ችግር የገንዘብን አነሳስ ታሪክና ዕድገት፣ እንዲሁም ባህርይና ሚና ካለመረዳት የተነሳ ነው። ይህ ማለት ግን የዓለም መገበያያ ገንዘብ አያስፈልገንም ማለቴ አይደለም። ለማለት የምፈልገው ለአገር ውስጥ የውስጥ ገበያ(Home Market) ዕድገት ዶላርና ኦይሮ ሳይሆኑ የአገራችን ብር ነው ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው።

ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግና፣ በማዕከለኛና በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተሰማርተው ለሚንቀሳቀሱ ገንዘብ ለማቅረብ የግዴታ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚተዳደር የብድርና የቁጠባ ባንክ መቋቋም አለባቸው። ይህ ዐይነቱ የባንኪንግ ሲይሰተም በህዝብ ዘንድ ያለውንና ጠቀሜታ ላይ የማይውለውን ወይንም ባልባሌ ቦታ ላይ የሚሰማራውን ገንዘብ በምርት ላይ ለማዋል የግዴታ የመንግስት ወረቀት(Bonds and Securities) በማቅረብ በዝቅተኛ ወለድ አማካይነት ከሰፊው ህዝብ ገንዘብ በመሰብሰብና ይህንን በጥናትና በዕቅድ መሰረት እንደገና ለአምራቾችችና በመዋዕለ-ነዋይ ለሚሰማሩ መልሶ በማበደር በገንዘብና በምርት መሀከል ያለውን ግኑኝነት ማጠንከር ይቻላል። ይህ ብቻ ነው ፍቱኑ የዕድገት መንገድ። ከዚህ በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚወጣውንና ወደ አገር ቤት ውስጥ የሚገባውን የውጭ አገር ገንዘብ መቆጣጠር ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት የሚሰበሰበው ገንዘብ የግዴታ ማሽኖችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማስመጣት ብቻ የሚውል መሆን አለበት። የቅንጦት ዕቃ ላይ የሚሰማራውን የውጭ ገንዘብ የግዴታ መቆጣጠር ሲገባ፣ ከውጭ በሚመጡ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።

በሰባተኛ ደረጃ፣ ምግብ ለስራ የሚል ልዩ ፕሮግራም ማቋቋም ያስፈልጋል። መንገድን፣ ድልድይን፣ ተምህርት ቤቶችን፣ የገበያ አዳራሾችን፣ ካናል ሲይሰተሞችን፣ ጋርደኖችንና ዛፎችን ለመትከል የግዴታ ስራ-ፈት የሆነውን ህዝብ በስራ ማሰማራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በስራ አማካይነት ብቻ ነው ብሄራዊ ሀብት ሊፈጠር የሚችለው። የስው ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ናቸው የሀብት ዋናው ምንጮች። ስለሆነም ይህንን ፋይናንስ ለማድረግ ማንኛውም አገር ቤት የሚኖረውም ሆነ  ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ገንዘብ በማዋጣት መሳተፍ አለበት። ይህንን መንገድ የምንከተል ከሆነ ኢትዮጵያን በሃያና በሰላሳ ዐመታት ውስጥ ልንቀይራት እንችላለን። ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ምሳሌ ልንሆን እንችላለን።

ስምንተኛ፣ የአገርን የተፈጥሮ ሀብትና የተትረፈረፈውን የሰው ኃይል በስራ ላይ ለማሰማራት የግዴታ የተቀላጠፉና ዘመናዊ የሆኑ ተቋማትን(Institutions) በአገር አቀፍ ደረጃ መገንባቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያም ዘመናዊና ብቃትነት ያላቸው፣ እንዲሁም ህዝብ የሚመካባቸውና ብሶቱን የሚያሰማበት ተቋማት የላትም። ያሉት ተቋማት በጣም ደካማ ከመሆናቸው የተነሳ በየክልሉና በየወረዳው እንዲሁም በትናንሽ ከተሞች ስራ ፈቶ የሚቀመጠውን የሰው ኃይል ለማንቀሳቀስ በፍጹም አይችሉም። የአንድ አገር መኖርና ህብረተሰብም ተከታታይነት ሊኖረው የሚችለው ዘመናዊና የተከበሩ ተቋማት ሲኖሩት ብቻ ነው። በየቦታው ያሉት የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ኢንስቲትሽኖች ግርማ ሞገስ የሌላቸው ናቸው። ለአንድ አገር ክብር የሚያሰጡ አይደሉም። ከዚህ ባሻገር በየቦታው ብቃትነት ያላቸው ተቁማት ባለመኖራቸው የተነሳ የውጭ ኃይሎች በየቦታው በቀላሉ ለመዘዋወርና የአገርን ብሄራዊ ነፃነት የሚያደፈርስ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝባችን ሊከበርና እንደሰው ሊታይ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የጠንካራ ተቋማት መኖር ለሰላም መኖር በጣም አስተማማኝ ነው። ስለሆነም መንግስት በዚህ ላይ ጠንከሮ ብሎ መስራት ያለበት ጉዳይ ነው።

ዘጠነኛ፣ ተቋማት ብቃት እንዲኖራቸው ከተፈለገ አዲስ የሰው ኃይል ማሰልጠን ያስፈልጋል። አዲስ አስተሳሰብ ያለውና ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአገር ግንባታ እጅግ ያስፈልጋል። በግልጽ እንደሚታየው አንደኛውና መሰረታዊ ለአገር ዕድገት እንቅፋት የሆነው ጉዳይ ዲሲፕሊንነት ያለው፣ ኃላፊነተ የሚሰማውና በተቀለጣፈ መልክ የሚሰራ ቢሮክራሲያዊ ኃይል አለመኖሩ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በተለይም የሲቪል ቢሮክራሲው ብሄራዊ ስሜት የሌለውና እራሱን ከሰፊው ህዝብ አግሎ የሚኖር ነው። ብሄራዊ ባህርይ የሌለውና ንቃተ-ህሊናው ደካማ የሆነ ቢሮክራሲ በሰፈነበት አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት አይቻልም። ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየትና ቴክኖሎጂን መቆጣጠር የቻሉት በከፍተኛ ብሄራዊ ስሜት በመነሳሳት ነው። ራሳቸውን ላለማስደፈር ቀን ከሌት በመስራታቸው ነው። በሌላ ወገን ግን በእኛ አገር ኃላፊነትን መወጣት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በማይታወቅበት አገር አንድ ሚኒስተርም ሆነ የበታች ሰራተኛ በቀን ከስምንት የስራ ሰዓት ውስጥ ጥቂቱን ብቻ ነው በስራ ላይ የሚያውሉት። ከብሄራዊ ስሜት መጉደል ሌላ፣ ሌላው ምክንያት የአገራችን ኢኮኖሚ ውስጣዊ ኃይሉ በጣም ደካማ በመሆኑ ቢሮክራሲው ላይ ጫና ማድረግ አይቻልም። ከዚህ ባሻገር አንድ ሚኒስተርም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናት ሚኒስተር መሆናቸውን ነው እንጂ የሚመለከቱት፣ የመቶ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል በእጃቸው ላይ እንደተንጠለጠለ በፍጹም የገባቸው አይመስልም። ከዚህ ስንነሳ ስለዘመናዊ አስተሳሰብ በሚወራበት ጊዜ የግዴታ ዘመናዊ አስተሳሰብ ያላቸውንና ኃላፊነት የሚሰማቸውን ሰዎች በተለይም ቁልፍ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ ሚኒስተሮች በተለይም የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስተሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲን ምንነት በቅጡ መረዳት አለባቸው። ከውጭ ኤክስፐርቶች ምክርን እየተቀበሉ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮረና ድህነትን ሊቀርፉ የሚችሉ አይደሉም። በአንጻሩ ድህነትን ፈልፋይ በመሆን የሰው ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት እንዲባክኑ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ጉዳይ ከአፄው አገዛዝ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና፣ ለድህነትና ለረሃብ ዋናው ምክንያት የሆነ የአስተሳሰብና የአሰራር ዘዴ ነው።፡ ባጭሩ እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ዘጠኝ ነጥቦች ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ የተቀላጠፈ ዕድገት ማየት እንችላለን። ህዝባችንም ብሄራዊ ስሜቱ መዳበሩ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ይተሳሰራል። መልካም ግንዛቤ !!

 

 

 

 

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ የዕድገት ኢኮኖሚክስ ምሁር ሲሆን፣ በርሊን በሚገኘው ፍሪ ዩኒቨርሲቲ፣በኢኮኖሚ ኮሌጅ፣ በመቀጠልም በቲክኒካልና በኢኮኖሚ ኮሌጅ ፣ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ፣ ስለዓለም አቀፍ ንግድ ፣ ስለ ዓለም አቀፍ ገንዘብና ስለ ዕዳና ጠንቅነቱ አስተምሯል። በተለያዩ ኢንስቲቱሽኖች ስለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ስለ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሚና

በየጊዜው ሰሚናር ይሰጣል። በጀርመን አገር የሚገኙ ኢምባሲዎችን ያማክራል። በቅርቡ „African Predicaments

and the Method of Solving them Effectively“  የሚል መጽሀፍ ጽፏል። በተጨማሪም በአማርኛ   „ካፒታሊዝም „  በሚል ርዕስ ስለካፒታሊዝም  ዕድገት መሰረተ-ሃሳቦችና አነሳስ ታሪክ መጽሀፍ ጽፏል። ከዚህ በተረፈ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ መጣጥፍፕችን ጽፎ ለአንባቢያን አቅርቧል። በተጨማሪም ለተለያዩ ውጭ አገር ለሚገኙ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያዎች ለብዙ ቃለ-መጠይቆች መልስና ማብራሪያ ሰጥቷል። በቅርቡ ለኢሳት የቴሌቪዥን ጣቢያ „ሰው ለመኖር የሚችልባትንና ሰዎችን ለማስተናገድ የምትችል አገር እንገንባ“  የሚል ሁለት ሰዓት የፈጀ የቃለ-መጠይቅ ማብራሪያ ሰጥቷል። 

                                 

                                fekadubekele@gmx.de