ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት ያልታነፀ የጦርነትና የስግብግብነት ምንጭ ነው፣ ባህልን ያወድማል፣ ሰፊውም ህዝብ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ያደርጋል!!

                                ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                              መጋቢት 27 2018(April 5, 2026)

ዕውቀት የሚባለው ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የምንጠቀምበት በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የፈለቀና በኋላም በአሜሪካን የተስፋፋ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች በሙሉ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አዲስ ዐይነት የፖለቲካ አወቃቀር ሲፈጠርና ዓለም አቀፋዊ ሲሆን በዘመናዊነት ስም ትምህርት የሚባለውን ነገር እንዳለ ነው የኮረጁት። ሲኮርጁም ዝም ብለው በጭፍን እንጅ የትኛው ነው ለተሟላ ወይም ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቸው? የትኛውስ ነው እዚያው እየተንደፋደፍን የሚያሰቀረን? እያሉና እያልን በማውጣትና በማውረድ አልነበረም። ከዚህም ባሻገር መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? ዋናው ተግባሩስ ምንድን ነው? አንድን አገር እንደ አገርና ህብረተሰብ በተሟላ መልክ መገንባት? ወይስ ወደ ተራ የመጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ ስልጣን ላይ ያለውን የገዢ መደብ ማስጠበቂያ? ፖለቲካስ ማለት ምን ማለት ነው? በተለይም እንደኛ ባለ አገር ውስጥ የመንግስቱ መኪና አወቃቀር ምንም ዐይነት ምሁራዊ ውይይትና ክርክር ሳይደረግበት፣ በተጨማሪም በመንግስትና በፖለቲካ መሀከል ያለው ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት ሳይብራራ ተግባራዊ የሆነው ከፖለቲካ አንፃር እንዴት ሊታይ ይችላል? ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ፖለቲካ ካለርዕይና ካለመሰረተ-ሃሳብ በጭፍን የሚካሄድ ነው ወይ? ወይስ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ነው? ባጭሩ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር ሳይነሱና ክርክርም ሳይደረግባቸው ነው እንደኛ ባሉት አገሮች ውስጥ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነትንና የመንግስትን መኪና የጨበጠውን ወደ ውንብድና የለወጡትና የሚለውጡት።

በአጠቃላይ ሲታይ ካፒታሊዝም እንደ ስርዓተ ማህበርና የኢኮኖሚ ስልት ሆኖ ብቅ ከማለቱ በፊት ትክክለኛና ትክክለኛ ያልሆነን ዕውቀት በሚመለከት ከሁለት ሺህ ተኩል ዓመት በፊት የጦፈ ክርክር ተካሂዷል። የእነ ሶክራተስና የእነ ፕሌቶ ክንፍ ትክክለኛ ዕውቀት ከጭንቅላታችን ውስጥ በማውጣትና በማውረድ፣ ወይም ራስን በማስጨነቅ የሚፈጠር ነው ሲሉ፣ ሶፊስቶች የሚባሉት ደግሞ ዕውቀት የሚገኘው ከምናያቸው፣ ከምንዳስሳቸው፣ ከምናሸታቸውና ከምንቀምሳቸው ነው የሚል ነው። ከዚህም በተጨማሪም የሶፊስቶች አካሄድ ዕውነተኛ ዕውቀትንና ሀቀኝነትን ለመፈለግና ለማስጨበጥ ሳይሆን በጥሩ ቃላት አሳምሮ በመናገር ነገሮችን አድበስብሶ ማለፍ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሶፊስቶች ሞራልንና ስነ-ምግባርን በሚመለከት ጥርት ያለ አቋም የላቸውም። እነዚህና እንደ ዕኩልነት የመሳሰሉት ነገሮች ከገዢው መደብ አንፃር የሚታዩና የገዢው መደብ የራሱን የበላይነት ለማስረገጥ ሲል የሚጠቀምበት ነው ይላሉ።

በአጠቃላይ ሲታይና ነገሩን ጠጋ ብለን ስንመለከት ምንም ዐይነት የማምረቻ ወይም ዛፍን የመቁረጫና ዲንጋይን የመፍለጫ መሳሪያዎች ከመኖራቸው በፊት፣ የሰው ልጅም እንደ እንስሳ ፍራፍሬ እየለቀመና እያደነም ነበር  ይመገብ የነበረው። ይሁንና ግን አንዳንዱ ብዙም ሳያወጣና ሳያወርድ(Intiutively) በቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ከዛፍ ፍራፍሬን እየለቀመና አራዊትን እያደነ በዚያው ብቻ ተወስኖ መኖር እንደማይችል ሲረዳ አንድ አካባቢ ረግቶ በመኖር የእርሻን ሙያ ቀስ በቀስ ማዳበር ቻለ። የአንትሮፖሎጂ ወይም የስልጣኔ ተመራማሪዎች እንደሚያስተምሩን የእርሻ ሙያ የመጀመሪያው የስልጣኔ መሰረት እንደሆነ ይናገራሉ።  ስለሆነም ፍራፍሬን እየለቀመና አራዊትነ በማደን ብቻ እየተመገበ ይኖር የነበረው ይህንን  አቁሞ እያረሰ ሲመገብ፣ እህሎችን እያዳቀለ የተሻሉ ዘሮችንም ሲያበቅልና ፍሬያማነቱም(Productivity) ሲጨምር ሲመለከት፣ በኋላ ላይም የስራ-ክፍፍልም(Division of Labour) ሲያዳብርና የንግድ ልውውጥም ሲደርግ፣ ከዚያም በኋላ ከተማዎች ሲቆረቁርና ሲሻሻሉም እነዚህን ሁሉ ማዳባር የቻለው በጭንቅላት አማካይነት በኢንቲዩሽን ነው ብለው ይናገራሉ። ትክክልም ነው። ምክንያቱም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ወደ ተግባር ለመመንዘር የሚያስችሉ የተጻፉ መመሪያዎች ስላልነበሩ ጭንቅላትን በማስጨነቅ በሙከራና በልምድ ነው እየተሻሻሉ ሊመጡ የቻሉት።  ከዚያ በኋላ ነው የዕውቀቶች አባት የሆነው ፍልስፍና ሊፈጠርና፣ ለተፈጥሮ ሳይንስና ለማቲማቲክስ ግኝቶች መንገዱን የጠረገው። በእርግጥም ታለስ ለሚባለው በአዮናውያን ደሴት በተለወደውና የመጀመሪያው የተፈጥሮ ፈላስፋ ተመራማሪ የነበረውና ከሱም በኋላ ብቅ ያሉት የተፈጥሮ ፍልስፍና ተመራማሪዎች ብቅ ማለት በጊዜው በአዮናውያን ደሴት እየጦፈ የመጣው የንግድ እንቅስቃሴ፣ የዕደ-ጥበብ ሙያ መዳበርና ወደነዚህ ደሴቶች፣ ማለትም ከተለያዩ ቦታዎች ከህንድና ከግብጽ ከሚመጡ ሰዎች ጋር በንግድ አማካይነት ግኑኝነት መፍጠርና እዚያው መኖር ለመጀመሪያው የተፈጥሮ ፍልስፍና ተመራማሪዎች ተፈጥሮን ለመቃኘትና ለማሰብ እንደረዳቸው መገንዘብ ይቻላል። ይህም የሚያረጋግጠው ከአንድ ጎሳ ብቻ የወጣና ለብዙ መቶ ዓመታት ከሌሎች ህዝቦች ተገልሎ ወይም ተነጥሎ ብቻውን የሚኖር ተፈጥሮን የመቃኘት ኃይሉና ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃም ለመሸጋገር እንደማይችል ነው፤ ዕውቀትንም አያፈልቅም። ይህ ብቻ ሳይሆን ቋንቋን በሚገባ በሰዋሰው መልክ አያዳብርም፤ አዳዲስ ፊደላትንም በማፍለቅና መልክ በመስጠት የመጻፊያና የመነጋገሪያ፤ እንዲሁም የመግባቢያ ቋንቋ የማድረግ ኃይል ሊኖረው አይችልም።

ለማንኛውም  የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላሳፋዎችም ለምርምራቸው አትኩሮ የሰጡት ተፈጥሮ እንዴት ልትፈጠር ቻለች? ተፈጥሮስ የምን ምን ነገሮች ውጤቶች ናት? ተፈጥሮንስ ምን ምን ነገሮች ሊያያይዟት ቻሉ? ይህ ብቻ ሳይሆን ወደሰማይ ላይ ሲመለከቱ ምን ምን ነገሮች ናቸው ኮከቦችን የያዟቸው? ለምንስ ፕላኔቶችና ኮከቦች ወደ መሬት በመውረድ አደጋ አያደርሱም? በማለት ነበር ራሳቸውን ያስጨንቁና ይጠይቁ የነበረው።  በጊዜው በተለያዩ የግሪክ ደሴቶች በሚኖሩ በተለያዩ ጎሳዎች ዘንድ በተለይም በመሪዎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ስለነበሩ በኋላ ላይ ለተነሱ እንደነሶክራተስና ፕሌቶ ለመሳሰሉት ፈላስፋዎች ምርምራቸውን የበለጠ በሰው ጭንቅላት ላይና በነበረው ስርዓት ላይ እንዲያተኩሩ አስገደዳቸው። በእነሶክራተስና በፕሌቶ ምርምር ተፈጥሮና በኮስሞስ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ፕላኔቶች መሰመራቸውን ይዘው ሳይጋጩ በፀሀይ ዙሪያ የሚሸከረከሩ ከሆነ የሰው ልጅ በተለይም የገዢ መደቦች ለምንድን ነው ርስ በርሳቸው የሚነታረኩትና የመጨረሻ መጨረሻም ወደ መገዳደል የሚያመሩት? ብለው በመጠየቅ አትኩሮአቸውን ይበልጥ በጭንቅላት ላይ ማድረግ ተገደዱ። በፕሌቶን ዕምነት የሰው ልጅ ዋናው ችግር ከትክክለኛ ዕውቀት ጋር ባለመተዋወቁና ጭንቅላቱም በደንብ ያልተገራ ስለሆነ የግዴታ አርቆ የማሰብ ኃይል ይጎድለዋል። በተለይም ስልጣን ላይ የተቀመጡ በስልጣንና ሀብትን በማካበት ስለሚያዙና ስለሚቋምጡ አትኩሮአቸውም በዚህ ላይ ስለሆነ ዋናው ተግባራቸው ጦርነትን ማካሄድ ይሆናል ይላል። ትክክልም ነው። ስለሆነም ይላል ፕሌቶ የሰው ልጅ ራሱን እንዲያውቅ ከተፈለገና ቁም ቁም ነገሮችን ይሰራ ዘንድ ማንኛውም ሰው በተለይም  ስልጣን ለመያዝ የሚፈልግ ወይም የፖለቲካ ዓለም ውስጥ ለመግባት የሚፈልግ ጭንቅላቱ ክልጅነቱ ጀምሮ በሚገባ መኮትኮት አለበት። የተለያዩ ፍራፍሬዎችን የሚያመርቱ ዛፎች ፍሬያማ እንዲሆኑና ጥሩ ጣዕምም እንዲሰጡ ከተፈለገ ከተተከሉበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ የሰውም ልጅ ከልጅነቱ ጀምሮ ከጥሩ ጥሩ ዕውቀቶች ጋር መተዋወቅ አለበት። አትክልቶች ከመሬት በሚያገኙት ንጥረ-ነገሮችና ከፀሀይ ከሚያገኙት ሙቀት ጋር ተደምሮ ፍሬያማ በመሆን ተለቅመው ይበላሉ። የሰው ልጅም ቀሰ በቀስ በሂደት በልምድና በሙከራ በማዳበርና ተፈጥሮን በበለጠ በመቃኘት የመጀመሪያውን የስልጣኔ መሰረት ለመጣል ቻለ። ከዚያ በኋላ ዕውቀት የሚባለው በተለያዩ ነገሮች የሚገለፀው፣ የዕውቀቶች አባት የሚባለውና፣ ከዚያም በኋላ የተፈጥሮ ሳይንስና ማቲማቲክስ እንዲሁም በጣም የሚያማምሩ የግንባታ ስራዎችና መናፈሻዎች በሙሉ በሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ነው የተሰሩት። ይህም ማለት የሰው ልጅ አስፈላጊው ነገሮች እንደመሰረት ከተጣሉለትና በጥሩና በተገለጸለት አሰተማሪ ትክክለኛውን ዕውቀት እንዲጎናፀፍ መንገዱን ካሳዩት ስራው ሁሉ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን መስራት ይሆናል።

ስለሆነም ከልጅነቱ ጀምሮ ከትክክለኛው ዕውቀት ጋር የተዋወቀና በአዋቂና ትክክለኛን ዕውቀት በሚያስተምር አስተማሪ የሰለጠነ ሰው አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠርና ለሌላውም በማስተማር ዕውነተኛ ሰው መሆኑን ያረጋግጣል። በሌላ ወገን ግን ሶፊስታዊ ወይም ማጨበርበሪያ በሆነ ዕውቀት በሚመስል ነገር የሰለጠነ ጭንቅላት ስራው ሁሉ ስግብግብነትና ጠብን መጫር ይሆናል። ይህ ጉዳይ በተለይም በአውሮፓው የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የታየና የመጨረሻ መጨረሻም ስልጣኔዎች እንዲወድሙ ያደረገ ነው። ስለዚህም ነው ጭንቅላታቸው በተሳሳተ ዕውቀት የሰለጠኑ እንደ አጋጣሚ ስልጣን ላይ በመውጣት ቀድሞውኑ ጭንቅላታቸው በተበላሽ ነገር የተጠመደ ስለነበር ስራቸው በሙሉ ተንኮል መስራት፣ አንዱን ማራቅ፣ ሌላውን በተለይም የሚያጎበድደውንና እሺ የሚለውን በማቅረብ የመንግስታዊ መኪና ሙልጭልጭ ባሉ ሰዎች እንዲያዝ በማድረግ የመንግስትን መኪና ወደ ተንኮል መስሪያና፣ እንዲያም ሲል ወደ ጦርነት መሳሪያነት በመለወጥ  በሰላም ለመኖር የሚፈልገውን ተራ ህዝብ ጦርነት ውስጥ በመዝፈቅ ፍዳውን ሲያሳዩት የቆዩት። የህም የሚያረጋግጠው  ጭንቅላታቸው በተንኮል፣ በስግብግብነትና በጦርነት የተጠመደ መሪዎችና ለስልጣን የሚቋምጡ ንዑስ ከበርቴዎች የሰው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን ልዩ ልዩ ባህርዮች አልያዙም ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነት ሰዎችም  የእግዚአብሄርን መንገድ የጣሱ በመሆናቸው መንፈሳቸው ሰይጣናዊ ስራዎችን መስራት ብቻ ነው። ምክንያቱም ዋናው ተግባራቸው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረውን እነሱን የሚመስለውን የሰው ልጅ የሆነ ያልሆነ ሰበብ በመፈለግ ፍዳውንም ማሳየት ነው። ይህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብና ሌላውን አምሳያቸውን ማሰቃየት በተለይም የስልጣን ማማ ላይ ቁጥጥ ባሉና በወታደሮችና በስለላ ኃይሎች በመታጀብ የፈለጉትን ነገር ማድረግ የሚችሉ ስለሚመስላቸው ስራቸው ሁሉ ውዝግብን መፍጠርና ሰላም የሚፈልገውን ህዝብ በሰላም እንዳይኖርና እየተጨነቀም እንዲኖር ማድረግና  ለበሽታም መዳረግ ነው። ከሌላው የተሻልኩ ነኝ፣ ኃይልም አለኝ በማለት የሰውን ልጅ መጨረሻ መሳሪያዎች በየጊዜው እንዲመረቱ በማድረግ በሌላው ይቀናቀነኛል ብለው በሚጠረጥሩት አገር ወይም ሰው ላይ ምንም ሳይነኩ ከአገራቸው ጠረፍ ተሻግረው በመሄድ በሌላ አገርና ህዝብ ላይ ጦርነት ይከፍታሉ። በተለይም ካፒታሊዝም ካደገና ከተስፋፋ ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ሌሎችን አገሮች መውረርና ሰውንም መግደል፣ እንዲያም ሲል የጥሬ-ሀብታቸውን በመዝረፍ ዕድገታቸውን ማቀጨጭ የተለመደ ተግባር ሆኗል። ይህ ዐይነቱ የተፈጥሮንና የእግዚአብሄርን ህግ የሚጥስ አካሄድ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነቱን ከተቀዳጀ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ ቅጥ ያጣ ሆኗል። በተለያዩ አገሮች ውስጥ የመንግስትን መኪና በሚቆጣጠሩ የፖለቲካ ኤሊቶች ነን ባዮችን በመጠቀምና የእሱ አጎብዳጂዎችና ጥቅም አስጠባቂዎች በማድረግ በተለይም የረጅም ጊዜ ታሪክና ጥሩና ጥንታዊ ባህል ያላቸውን አገሮች ያምሳል። እንደሚታወቀው አሜሪካ እንደ አገር የተመሰረተውና ወደ ኃያልነትም የተለወጠው ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተሰደው በሄዱ ሰዎች አማካይነት ነው። እነዚህም አውሮፓውያን አሜሪካን ሲደርሱ ቀደም ያለ ስልጣኔ ያላቸውን እንዲያኖችን ያገኛሉ። ከእንዲያኖች ጋር በመቀላቅልና የነበራቸውን ስልጣኔ በመውሰድና በመልመድ፣ እንዲሁም በማሻሻል አብረው መኖርና ወደ መሻሻል ማምራት ሲገባቸው ወድ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ እንዲያኖችን ያርዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ከአፍሪቃ ተሸጠው የመጡ አፍሪቃውያንን ወደ ባርነት በመለወጥና በፕላንቴሽን ስራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ይበዘብዟቸውና ማሰቃየትንም ተያያዙ። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተውጣጥተው የሄዱ ሰዎች በሶስትና በአራት ሺህ ዓመት ሲወረድ ሲዋረድ የመጣ ታሪክ እንዳልነበራቸውና፣ በድሮው፣ በአሁኑና በሚቀጠለው ዘመን ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት እንደማይረዱ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ነገሮችን ሁሉ ከዛሬው አንፃር ብቻ የሚያዩና ሁሉንም ነገር በመጨፍለቅ አንድ ወጥ ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በመሰረቱ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚጥስ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ አካሄድ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳስበም በአውሮፓ ምድር በተለይም በፖለቲካ፣ በሚሊተሪ፣ በስለላና በኒዎ-ሊበራሊ ኢኮኖሚስት ኤሊቶች ዘንድ የተስፋፋ በጣም አደገኛ አስተሳሰብ ነው። የቅኝ ግዛትና የቅኝ እጅ አዙር አገዛዝም ከዚህ ዐይነቱ ሁሉንም ነገር በራስ ቁጥጥር ስር በማምጣትና የተለያዩ አገሮች ህዝቦችን ባህሎች በመደምስስ ተገዢና አጎብዳጅ፣ እንዲሁም ተበዝባዥ ማድረግ ነው። በዚህም አማካይነት በየአገሮች ውስጥ ጤናማና የተለያዩ ባህሎችን ያጣመረና ሰብአዊነት ያለው ጤናማ ማህበረሰብ ወይም ህብረትዘሰብ ቀስ በቀስ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ  የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቅጥ ያጣ አካሄድና አገሮችን በማመስ ሰውን መጨረስ እንደዘመናዊነት ወይም እንደ ስልጣኔ በመታየት ተቀባይነትን ለማግኘት ችሏል። በተለይም እንደኛ ባለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊተሪና የስለላ ኢትዮጵያውያን ኤሊቶች ዘንድ ተቀባይነትን ያገኛና የተተገበረም ነው፤ የሚተገበርም ነው። አገራችንም  ከሃምሳ ዓመታት በላይ ልትታመስና ባህሏም ሊፈራርስና ወደ ብልግና መድረክም ለመለወጥ የቻለችው በተበላሸ ዕውቀት በሰለጠኑ ግለሰቦችና የስልጣንን ማማ በተቆናጠጡ ስግብግብ ሰዎች አማካይነት ነው። እነዚህና በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ ስልጣንን የተቆናጠጡ ኤሊቶች፣ የወታደር መኮንኖችና ጄኔራሎች፣ እንዲሁም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሰለጠኑ ምሁራን ነን ባዮች ሁሉንም ነገር በመቆጣጠር ማዕከለኛውና ደቡብ አሜሪካንን የወንበዴዎችና የድረግ መሸጪያ መድረክነት ለውጠዋቸዋል። በዚያው መጠንም ባለፉት ስድሳ ዓመታት የተሻለ አስተሳሰብ ያለው ምሁር ብቅ እንዳይል ለማድረግ በቅተዋል።  ይህም ማለት አንድ ፓርቲ ወይም ግለሰብ ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ ካለምንም ተቀናቃኝ ወይም የተሻለና አማራጭ አስተሳሰብ ሳይሰነዘር ሰፊውን ህዝብ የሚጎዳ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ይሆናል። በሚሌ የሚመራውን የአርጀንቲናን ሁኔታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። በአሁኑ ወቅት 50% የሚሆነው የአርጀንቲና ህዝብ ከድህነት ወለል(Below poverty line) በታች የሚኖርና ሰፊው ህዝብም ለድህነትና ለበሽታ የተጋለጠበትን ሁኔታ እንመለከታለን።

የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ሰበቦችን እየፈለገ የሚያካሂደው ወረራና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችንም መግደል የዚህ ዐይነቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቅጥ ያጣ የስግብግብነትና ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አለብኝ ከሚለው ስሜት የተነሳ ነው። ለእሱ ያደሩ ግለሰቦችን በገንዘብ በመደለል በእየገሮች ውስጥ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ ሶሪያና አፍጋኒስታን፣ እንዲሁም ዩክሬይን ያካሄደው ጦርነትና ስልጣን ላይ ያወጣቸው ሰዎች ዲሞክሲያዊ ስርዓትን ለማምጣት የሚችሉ ሳይሆኑ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምም ፍላጎት አይደለም፣ የየአገሩን የጥሬ-ሀብት፣ በተለይም ዘይትን ለመቆጣጠርና ለመዝረፍ ብቻ ነው። አፍጋኒስታን ውስጥ ስላልተሳካለት ከ20 ዓመት ጦርነት በኋላ ታሊባኖች ስልጣንን በመቆጣጠር ኋላ-ቀር ፖለቲካ እንዲያካሂዱ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። በሌላ ወገን አፍጋኒስታን በ1950ዎቹ፣ 60ዎቹና 70ዎቹ ዓመታት የሰለጠነ ሁኔታ የሰፈነባት አገር ነበረች። ይሁንና ስቭየቶችን ለማስወጣት ሲል እነቢላዲንን በ$500 ሚሊዮን የደገፈውና በመሳሪያም ያስታጠቃቸው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊም የመጨረሻ መጨረሻ ላይ አፍጋኒስታንን ወደ ጦርነት መድረክ በመለወጥ የኋሊት ጉዞ እንድትጓዝ ለማድረግ በቅቷል። በየካቲት 28፣ 2026 ዓ.ም እስራኤልንና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነትና ለብዙ ሺሆች ሰዎች መሞትም ምክንያት የሆነው የዚህ ተቀጢላ ውጤት ነው። በኢራን ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ሳይሆን የአሜሪካኑ ፕሬዚደንት ትረምፕ ሳያፍር እየደጋገመ እንደተናገረው የኢራንን የዘይትና የጋዝ ክምችት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ብቻ ነው። ባለፉት የ35 ቀናት ጦርነት ጊዜ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ሲገደሉ፣ የሶስት ሺህ ዓመታት የታሪክ ቅርሶች አንዳንዶቹ እንዳሉ ወድመዋል። ወጣት ሴቶች የትምህርት ገበታ ላይ እንዳሉ ተገድለዋል። ይሁንና በደንብ የተዘጋጀው የአያቶላሆች መንግስት አፀፋውን በመመለስ በአካባቢው ያሉ የአሜሪካን የጦር ካምፖች የሰፈረባቸውን  እንደ ባህርይን፣ ካታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ኢሚራት፣ በተለይም ዱባይን በሚገባ ደብድቧል። ቴላቢብ፣ ሃይፋና ጄሩሳሌምም ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው የእስራኤል የስለላና የጦር መኮንኖች በብዛት ተገድለዋል። በአይረን ዶም ትመካ የነበረችው እስራኤል ጉድ በመሆን ከጎረቤት አገሯ ጋር የማያስፈልግ ጦርነት በመክፈት በቀላሉ የማትወጣው ችግር ውስጥ ገብታለች። በከተማዎች ውስጥ የሚኖረው ህዝቧም በፍርሃት በመመሸጊያ ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። የቻለው ወደ ሳይፐርስና ወደ ሌሎች አገሮች ተሰዷል፤ በመሰደድም ላይ ነው። ይህ አላስፈላጊ ጦርነት ይኸው እንደምናየው በከፍተኛ ደረጃ የዘይትንና የጋዝን ዋጋ በማስወደድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስን እያስከተለ ነው። ወደ አረብ አገሮች በተለይም ወደ ዱባይ እንደፈለጉት የሚመላለሱ ቱሪስቶችና ባለሀብታሞች እንደፈለጋቸው እንዲወጡና እንዲገቡ አልቻሉም። በቱሪዝምና በጥቁር የገንዘብ ማሽሸ የናጠጠችው የተባበሩት የአረብ ኢሚራት ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ወድቃለች። ሆቴልቤቶም ደንበኛ በማጣት ገበያቸው በከፍተኛ ደረጃ ቀዝቅዟል። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው ፖለቲከኛ ነን ባዮች አርቀው ማሰብ እንደማይችሉ ነው። በተሳሳተ ዕውቀትም የሰለጠኑና ከዕውነተኛ ዕውቀትም በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ርቀው ስለሚገኙ ስልጣናቸውን ለማጠናከር፣ የሌሎች አገሮችን የጥሬ-ሀብት ለመዝረፍና የበላይነታቸውን ለማሳየት ሲሉ ብቻ በሰላም ለመኖር የሚፈልገውን ህዝባቸውን የማያስፈልግ ወጥመድ ውስጥ ይከቱታል። በመሰረቱ በእየ አራት ዓመቱ አዳዲስ ገዢዎች የሚመረጡት አገራቸውንና ህዝባቸውን በስርዓት ብቻ ለማስተዳደር እንጂ በሌሎች አገሮች ላይ ጦርነት በመክፈት የራሳቸውን ህዝብ ጭንቀት ውስጥ ለመከተትና ሌሎች አገሮችንም ለማመስ አይደለም። በህገ-መንግስታቸውና በፓርቲዎች ፕሮግራም ውስጥ ጦርነት ማካሄድና ሌሎች አገሮችን ማመስ አለብህ ተብሎ አልተጻፈም። ቢጻፍም እንኳ እያንዳንዱ አገር ነፃ ስለሆነ ኃይለኛ ነኝ በሚል መንግስት ጦርነት እንዲከፈትብት አይገባም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና አካሄድ እነ ፕሌቶ ቀደም ብለው እንዳሳሰቡት የፖለቲካ ስልጣን በስልጣንና ሀብት በማካበት በቋመጡ ሰዎች እጅ ከወደቀና፣ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችም በተሳሳተ ዕውቀት በሚመስል ከሰለጠኑና በዚህም የሚመሩም ከሆነ ዋናው ተግባራቸው ዘረፋና ጦርነትን ማካሄድ ብቻ ይሆናል። የሌሎችን አገሮች የታሪክ ቅርስ ድምጥማቱን በማጥፋት የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር አንድ ዐይነት አስተሳሰብ፣ ይኸውም የስግብግብነትና ባህለ-ቢስ አኗኗር እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። ይህም ማለት ማንኛውም ሰው፣ በተለይም የፖለቲካ ስልጣንን የሚይዝ፣ ወይም ቀድሞውኑ ስልጣንን የያዙ ሰዎች ጭንቅላታቸው በሳይንሳዊ ዕውቀት ያልተኮተኮተ ከሆነ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በሙሉ ጥፋት ይሆናል ማለት ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ እነ ፕሌቶ ያሉት ትክክል ነው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን በጥሩ ዕውቀት ከኮተኮተ ከማንኛውም ዕቡይ ስራ በመቆጠብ ለሰው ልጅ የሚጠቅሙና ኑሮዎንም የሚያቃሉለት አዳዲስ መሳሪያዎችን ይፈጥራል። ቀስ በቀስም እንዳይጎዱት ውበትና የተሻለ ቅርጽ በመስጠት የመስራት ኃይሉን ያሻሽላል። ሰለሆነም ሰው መሆኑን ያረጋግጣል። የተፈጥሮ ፈላስፋ አባት ታለስ እንዳለው ከሁሉ ነገር ደስ የሚለኝ ሰው ሆኜ በመፈጠሬ ነው። የማሰብ ኃይልም ስላለኝ አዳዲስ ነገሮችን በመስራት ሰው መሆኔን አረጋግጣለሁ። ስራዬም ሁሉ ቀና ነገርን ማሰብ ብቻ ነው ይላል። ስለሆነም ትክክለኛ ዕውቀት በማሰብ ኃይል የሚገኝና ወደ ተግባርም የሚለወጥ ነው። ይህ ማለት ግን የምናያቸው፣ የምንጨብጣቸው፣ የምንዳስሳቸውና የምናሸታቸው ነገሮች ምንም ሚና የላቸውም ማለት አይደለም። ለማንኛውም ዕውቀትን አስመልክቶ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በእንግሊዝና በጀርመን ፈላስፋዎች መሀከል የጦፈ ክርክር ተካሂዷል። የእንግሊዞቹ ፈላስፋዎች ዕውቀት በቀጥታ ከምናየው፣ ከምንዳስሰው፣ ከምናሸተውና ከምንቀምሰው የሚገኝ ነው ሲሉ፣ የጀርመኖቹ ፈላስፋዎች የእነ ፕሌቶንን መንገድ ይከተሉ ነበር። ከጀርመን ፈላስፋዎች ውስጥ ካንት የሚባለው ሁለቱንም አካሄዶች ለማስታረቅ በመሞከር በተለይም የአርቆ-አሳቢነትን ሚና አጥብቆ ያነሳል። ይህም ማለት በቀጥታ የምናያቸውን ነገሮች ጠጋ ብለን በመመራመርና በመረዳት በማሰብ ኃይላችን ከነበራቸው ጥሬ ሁኔታ በማሽን በመታገዝ ወደ ተጠቃሚነት ልንለውጣችው እንችላለን። ይሁንና ግን የጥሬ ሀብቶችን ወይም የአንድን ዛፍ ውስጣዊ  ባህርይ መረዳት አለብን። ለምሳሌ ማንኛውም የዛፍ ዐይነት ለሳንቃ፣ ለጠረቤዛና እንደዚሁም ለቤት መስሪያነት አያገለግልም።  ከእነዚህ ውስጥ ባህርዛፍን ብንወስድ ለሳንቃ፣ ለጠረቤዛና ለቤት መስሪያ የሚያገለግል አይደለም። ለሳንቂያ፣ ለጠረቤዛና ለወንበር መስሪያ የሚያገለግሉ ዛፎች እንደ ዋርካና ዋንዛ የመሳሰሉት ናቸው። ሌሎችም ዛፎች እንደዚሁ አሉ። ባህርዛፍን ለወረቀት መስሪያ መጠቀም ይቻላል። በተጨማሪም ለመድሃኒትነት የሚያገለግል ኤቴሪክ ዘይት ጨምቆ ማውጣት ይቻላል።

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱትን የአውሮፓ ምሁራን ምን ቢያስገድዳቸው ነው  በተለያዩ ነገሮች ላይ አትኩሮ በመስጠት ጥልቅ ምርምር እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው? አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስተምሩን ከሆነ ቀደም ብለውም ሆነ በኋላ ላይ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት ምሁራን በጊዜው የነበረውን ጠባብም ቢሆን አመቺ ሁኔታን በመጠቀም የግዴታ በተለያዩ ዕውቀቶች ላይ እንዲያተኩሩ ተገደዋል። በእነ ፕሌቶ ዘመን ለማንኛውም የማያዳላ አገዛዝና አትኩሮውም ለስልጣኔ የቆመ መንግስት እንደሚያስፈልግ ጠለቅ ያለ ውይይት ይካሄድ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ፕሌቶ እንደሚያስተምረን ማንኛውም ሰው በተለይም ፖለቲከኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ጥሩ ሰው መሆን አለበት ይለናል። የግሪኩ ስልጣኔ ከወደመ በኋላ 1500 ዓመታት ያህል የአውሮፓው ህዝብ በጨለማ ዓለም ውስጥ ይኖር ነበር። ሳይንሳዊ ምርምርን ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የኋላ ላይ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የግሪኩ ዕውቀት ወደ አውሮፓ ሲገባና ከግሪክ ቁንቋ ወደ ላቲን ሲተረጎም እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከዚህ ዕውቀት ጋር የተዋወቁ ምሁራን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ከጨለማው ዓለም ለመውጣት የሚቻልበትን መንገድ ይቀይሳሉ። ከዚያ በኋላም አዳዲስ ዕውቀቶች በመፍለቅ ስልጣን ላይ ያሉትን መፈናፈኛ ያሳጧቸዋል። በተለይም የልጣንንና የመንግስት አወቃቀርን ጠጋ ብለው ያጠኑት የእንግሊዝ ምሁራን ስልጣን በአንድ ግለሰብ ቁጥጥር ሰር መውደቅ የለበትም። የግዴታ የስራ-ክፍፍል በመዳበር ለጊዜው የመንግስትን መኪና የሚጨብጠውና ፖሊሲንም የሚያወጣው በህዝብ ተመራጮች ወይም በፓርሊያሜንት ቁጥጥር እየተደረገበትና የሰራውንም በሪፖርት መልክ በማቅረብ ተግባሩ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ያስተምራሉ። ከዚህም ጋር ተደምሮ በተለያዩ መስኮች የፓርሊሜንቴሪ አጣሪ ኮሚቴ በመቋቋም አንድ ሚኒስተርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስህተት ወይም ወንጀል ከሰሩ መጠየቅ አለባቸው። እንደ ወንጀላቸው ወይም ስህተታቸው ክብደትም አንድ ሚኒስተርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስተር ከስልጣኑ መወገድ አለበት። ይህም ማለት አንድ ሚኒስተርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስተር የተመረጥኩት ለአራት ዓመት ነው በማለት ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ የመቆየት መብት የለውም።  ባጭሩ የአውሮፓውን የዲሞክራሲ ግንባታና የፓርሊሜንተሪ ተቋም ስንመለከት ምሁራዊ እንቅስቃሴው ከአራትና ከአምስት መቶ ዓመት በፊት ቀደም ብሎ ነው የጀመረው። ይሁንና ብዙ ነገሮች ተግባራዊ መሆን የጀመሩት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ1945 ዓ.ም በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ሊሆን የቻለው ካፒታሊዝም በአዳዲስ ቴክኖሎኦጂዎች እየታገዘ ምርታማነትን ሲያሳድግና የውስጥ ገበያም ሲስፋፋም ሀብረተሰቡ በተለያዩ ፓርቲዎች ስር የመደራጀት ወይም የመሰባሰብ ዕድል አገኘ። አንዳንዶች አገሮችም እንደ ጀርመን የመሳሰሉት በፋሺዝም የአገዛዝ ዘመን የደረሰባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመገንዘብና ከዚያም በመማር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት መስኮች ባሻገር በየአካባቢው ህዝቡ ከስራ በኋላ እየሄደ የሚማርባቸው የህዝብ ትምህርት ቤቶች የሚሏቸውን በማቋቋም ዐይኑን እንዲከፍት ለማድረግ በቁ። ይሁንና በካፒታሊዝም ልቅ በሆነ መልክ መስፋፋት የተነሳ በተለይም እንደ አሜሪካ በመሰለው አገር አደገኛ ሁኔታን እንመለከታለን። በተለይም የፖሊሶችና የስለላ ተቋማት በግለሰቦች፣ በተለይም ከውጭ አገር መጥተው እዚያው ተዋልደው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚወስዱት አሰቃቂ እርምጃዎችን ስንመለከት የአሜሪካ የመንግስት መኪና አወቃቀር ጭንቅላታቸው ባልተገራና የጭንቅላታቸው ብሎንም በወላለቀ ሰዎች እንደተያዘ ለመረዳት ይቻላል። የመንግስትን አወቃቀርና ሚና ለመረዳት የፈለገ የፍልስፍና ጥናት ማካሄድ አለበት። በመንግስት ዙሪያም ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ጠለቅ ያሉ ጥናቶች እንደነ ሺለርና ቪሊሄልም ሁምቦልድት በመሳሰሉት ታላላቅ ምሁራን ተጽፎ ይገኛል።ከእነሱ አመላከትና አነሳስ ስንነሳ በካፒታሊስት አገሮችም ሆነ በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተቋቋሙት የመንግስት መኪና አወቃቀሮች በጣም ያበጡና የሰፊውን ህዝብ መብት የሚጋፉ ናቸው ማለት ይቻላል። ለዘረፋና ጥቂቱን ለማደለብና የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ የሚያግዙ ናቸው። ባለፉት 36 ዓመታት በአገራችን ምድር የተፈፀመውን ሁኔታ ጠጋ ብሎ መመርመሩ ተገቢ ነው። የህወሃትና የአቢይ አገዛዞች አገራችንን፣ ህዝባችንን፣ ታሪካችንና ባህላችንን እንደ ጠላትና እንደ ቆሻሻ ነገር በማየትና የብልግና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ የሚፈልጉትን ነገር ሰርተውላቸዋል፤ እየሰሩላቸውም ነው። እነዚህ ሁለት አገዛዞችና ሌሎችም ለስልጣን የሚቋምጡ ኤሊት ነን ባይ  ኢትዮጵያውያን በትላንት፣ በዛሬውና በነገው መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኘነት ባለመረዳት በህዝባችን፣ በታሪካችንና በባህላችን ላይ ዘመቻ አካሂደዋል፤ እያካሄዱም ነው።

ለማንኛውም በአጠቃላይ ሲታይ ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላና ሳይንስና ቴክኖሎጂንም ከተቆጣጠረ ወዲህ በትክለኛውና ትክክለኛ ባልሆነው ዕውቀት መሀከል ይደረግ የነበረው ክርክር ደብዛው እየጠፋ መጥቷል። በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ በዘመናዊነት ስም ለተሟላ ወይም ለሁለ-ገብ ዕድገት የማያመች ትምህርት በመቀረፁ በተለይም በሶሰተኛው ዓለም አገሮች፣ ኢትዮጵያም ጭምር መስፋፋት ጀመረ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ለተሟላ ዕድገት የማያመች የመንግስት መኪና አወቃቀር ተመሰረተ። የሚሊተሪ፣ የፀጥታ፣ የፖሊስ፣ የሲቪል ቢሮክራቶችና ቴክንክራቶች አሜሪካን አገር በመሰልጠን ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ለመያዝ ቻሉ። ይህ ዐይነቱ የመንግስት መኪና አወቃቀር መሬት ላይ ከሚታዩ የማቴሪያል ሁኔታዎች ጋር የማይወዳደር በመሆኑ ማበጥና ወደማስፈራሪያነት በመለወጥ ዕድገትን አፋኝና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳያብብ ለመደረግ በቃ። አላቪ የሚባለው የፓኪስታን ምሁር ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የመጣውን የመንግስት መኪና ማበጥ ከመጠን በላይ የተጋነነና የተሟላ ዕድገትንም የሚቀናቀን መሆኑን በሚገባ መልክ አትቷል። ስልጣንን የጨበጠው ኤሊትም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የሌሎች ኃይሎች ተላላኪ በመሆን በሳይንስና በቴክኖሎጅ የሚገለጽ፤ ውብ ውብ በሆኑ ከተማዎች የሚገለጽና በስራ-ክፍፍልም የዳበረ የውስጥ ገበያ(Home Market) እንዳያብብ ዋና ዕንቅፋት ለመሆን ቻለ።  በየአገሮች ውስጥ ስልጣንን የጨበጠው አዲስ ኤሊት የመንግስቱን መኪና በመቆጣጠርና በወፈፍራም ጄኔራሎች በመከበብ ዋናው ተግባሩ በህዝቡ ላይ ጦርነትን ማካሄድ ሆነ። ይህ ዐይነቱ የመንግስት መኪና አወቃቀርና ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም የአገዛዝ ስልት በሰፊው ህዝብ ዘንድ፣ በተለይም በጥቅም በተገዛው ኤሊት ዘንድ ተቀባይነትን በማግኘት እንደተፈጥሮአዊ ህግ ሆኖ ለመወሰድ በቃ።  ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ካፒታሊዝምና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሙሉ በሙሉ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን ከተቆጣጠሩ በኋላ ባስፋፉት ከዕውነተነኛው ወይም ፕላቶናዊ ዕውቀት የራቀ ጭንቅላትን የሚመርዝና ተንኮለኛና ስግብግብ የሚያደርግ ዘመናዊነት የሚሉት ትምህርት ከተስፋፋ ጊዜ ጀምሮ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ ከተፈለገ እነ ሶክራተስ፣ ፕሌቶ፣ አርስቴቶለስ፣ በኋላ ላይ ደግሞ የሬናሳንስ ሰዎች፣ ማለትም እንደ ዳንቴና ዳቪንቺ፣ በኋላ ላይም ጋሊሊዮና ኬፕለር፣ ቀጥሎም እነ ካንትና ሄገልስ፣ እንዲሁም ሁምቦልድት በመባል የሚታወቁት ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች፣ ከዚያም በኋላ ጋውስና ሪማን የሚባሉት በዕውቀት የተካኑና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መፈጠር መሰረት የጣሉት ሁሉ ብቅ ማለት የጀመሩት በጊዜው የሰብአዊነት ትምህርት በመባልና ጭንቅላትን በትክክል ዕውቀት በሚቀርጽ ዕውቀት ከልጅነታቸው ጀምረው በመሰልጠናቸው ብቻ ነው። ይህንን መረዳትና መተዋወቅም በጣም ጠቃሚም ነው። ይህንን ስንረዳ ብቻ ነው ከማስያፈልግ ውዝግብና ስድብ ልንቆጠብ የምንችለው።

ለማንኛውም ከግሪክ ስልጣኔ ጊዜ ጀምሮ ይህ ትክክለኛው ዕውቀት እየዳበረ ባይመጣና በአስረኛው ክፍለ-ዘመን በአረቦች አማካይነት ወደ አውሮፓ ምድር ባይገባና ወደ ላቲን በመተርጎምና ባይስፋፋ ኖሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች በፍጹም ባልዳበሩ ነበር። እንደነ ሬኔ ዴካ፣ ኒውተንና ላይብኒዝ እንዲሁም አያሌ የማቲማቲክስና የፊዚክስ ሰዎች ብቅ ማለትና በመሰልጠን የሳይንስንና የቴኮኖሊጂን መሰረት ባይጥሉ ኖሮ የሰው ልጅ እንደ አውሬ ወይም እንደ እንስሳ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተዘዋወረ የሚኖር ፍጡር ነበር ማለት ይቻላል። እነዚህን የመሳሰሉ ታላላቅ ሳይንቲስቶችና የማቲማቲክስ ሰዎች ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሲያፈልቁና ሲያዳብሩ ዋናው ዓላማቸውም የሰውን ልጅ ከጨለማ ኑሮ በማውጣት ብርሃንን እንዲይይ ለማድረግ እንጂ የተወሳሰቡ የጦርነት መሳሪያዎችንና አቶም ቦምብን በመሰራት የሰውን ልጅና ተፈጥሮን ለማውደም አለነበረም። ይሁንና በካፒታሊዝም አይሎ መውጣትና ወደ ኢምፔሪያሊዝምነት´ መለወጥ የተነሳ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ህይወት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ቢያቃልሉም፣ ለጥፋት የሚሰሩት የተዋሰሰቡ የጦር መሳሪያዎች የዕውነተኛ ዕውቀትንና እንዲያም ሲል የኑሮን ትርጉም እንድናጣ ለማድረግ በቅተዋል። በተለይም የፖለቲካ ስልጣንን የሚጨብጡ ገዢዎች በህግ-የበላይነት ሽፋን ስር ሰፊውን ህዝብ ከማንኛውም ውሳኔና ክርክር በማግለል ሁሉንም ነገር ራሳቸው ወሳኝ በመሆን የየአገራቸውን ህዝቦች ማሳቀያና ሀብትም ማሸጋሸጊያ መንገድ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በጊዜው በጥንታዊቱ የግሪክ ስልጣኔ ዘመን እነ ፕሌቶ ጠጋ ብለው የተመለከቱት ሁኔታ አሁንም በግልጽ ይታያል። የግሪኩ ስልጣኔ ቀስ በቀስ ሊፈራርስ የቻለው በጊዜው የአቴኑ ገዢ ፕረክለስ የተባለው የተሳሳተ ዕውቀትን በሚያሳፋፉና ሀብትን በማካበት ላይ ባተኮሩ ሶፊስቶች ተብለው በሚታወቁ ምሁራን ነን ባዮች በመከበቡና ዋናው ተግባሩም ጦርነትን ማካሄድ ስለነበር የመጨረሻ መጨረሻ ሊገረሰስ ቻለ። ቀስ በቀስም የግሬኩ ስልጣኔ በመፈራረስ ግሪክ በሮማውያን ወራሪዎች በመወረር ስልጣኔዋ ሊወድም ቻለ። ባጭሩ ዛሬም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮች የሚያደርጉት ድርጊት በሙሉ በሶፊስቶች የተከበበውን የፕሬክለስን ዐይነት ድርጊት ይመስላል። በትክክልም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችም የጄኦ-ፖለቲካ በሚባሉ ጦርነትን የሚያስፋፉ የፓለቲካ ምክር በሚሰጡና፣ በአገርም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፈ ደረጃ ለዘረፋና ለሀብት ሽግሽግ፣ እንዲያም ሲል ያልተስተካከለ ዕድገት በማስፋፋት የየአገሩ ህዝብ ብዥ ብሎበት እንዲኖር የሚያደርገውን ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት በየአገሩ ውስጥ እንዲተገበሩ በማድረግ 90% የሚሆነውን ህዝብ እያደኸዩት ነው። ባጭሩ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችና እንደኛ የመሳሰሉት አገሮች የመንግስት መኪናዎች በአጭበርባሪዎችና በሀብት ዘራፊዎችና በአዘራፊዎች የተያዘ ነው። ይህም ሆን ተብሎ የሚካሄድና በየአገሩ ያለው ሰፊው ህዝብ እንደ እንስሳ እየተነዳ እግዚአብሄር የሰጠውን የማሰብ ኃይል በመጠቀም ውብ ውብ ነገሮችን በመስራት በስምምነት ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ እንዳይመሰርት የተሸረበ ከዕውነተኛው ዕውቀት በብዙ ሚሊዮን ማይልሶች የራቀ ጥቂቱን ሰይጣን ወይም ጭራቅ የሚያደርግ ዕውቀት የሚሉት ነገር ነው። ስለሆነም የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ፣ የስለላና የኢኮኖሚስት ኤሊቶች በዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ ዕውቀት በሚመስል ነገር በመሰልጠናቸው ተግባራቸው አንድ ጥበባዊና ጠንካራ አገር መገንባት ሳይሆን ዋናው ተልዕኮዋቸው ጦርነትን ማካሄድ፣ የብልግና ኢንዱስትሪን በማስፋፋት የአገርን ባህል ማውደምና ሰፊውን ህዝብ ግራ ማጋባት ዋናው ተግባራቸው ሊሆን በቅቷል። ይህንን ዐይነቱን አካሄድ የሚቃወምና ቀናውንም መንገድ ለማስተማር የሚጥር እንደ ኮሙኒስት ወይም ማርክሲስት በመፈረጅ  የፍየል ወጤ እናዘምትብሃለን እየተባለ ማስፈራርት ዋናው ተግባር ሆኗል። ይህ ዐይነቱ ማስፈራራት ወይም ዘመቻ ጥንትም የነበረና በተለይም የካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነትን በተቀዳጀበት ዘመን የአመራሮችን ፈለግ የጣሰና ሳይንስዊውን መንገድ በትክክል የሚያሳይ ሁሉ ከእነነፍሱ የተቃጠለበት ዘመን በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በአሁኑ ዘመንም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮች የወዳጅ ጠላት ፖለቲካ የሚለውን ፈሊጥ በማስፋፋትና በውጭም ሆነ በየአገሮች ውስጥ ቡችላዎቻቸውን በመኮትኮት ፍዳችንን እያሳዩን ነው። የሚገርመው ነገር ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በየዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ በመስፋፋቱ በአመለካከታቸው የተነሳ ብዙ ምሁራን  ከማስተማር ተግባራቸው እንዲነሱ በመደረግ ለሌላ አማራጭ ስራ ተጋልጠዋል። በየዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ በተለይም በሶሻል ሳይንስ ዴፓርትሜንት እንደ ኒዎ-ሊበራሊዝምና የጦረኝነት የጂኦ-ፖለቲካ አስተሳሰብ በመስፋፋቱ ትክክለኛውንና ግንዛቤ የሚሰጠውን ትክክለኛ ዕውቀት ማስተማር በፍጹም አይቻልም። በተለያዩ ስብሰባዎችም ላይ የራስን አስተያየት ለመስጠት ከተሞከረ መጮህ ይጀመራል።

በአጭሩ ለማለት የምፈልገው ከስድሳዎቹ ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የተፈጠረው የተማሪው እንቅሰቃሴና፣ የኋላ ላይም የብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች የሚሏቸው ሁሉ የተዘበራረቀውና ያልተሟላው ዕድገት ውጤቶች ናቸው። ስልጣንንም የያዙት በተመሳሳይና በተበላሽ አሳተሳሰብ በመኮትኮታቸው ከአርቆ አሳቢነት ይልቅ የማንአለኝበትና የችኮነት ባህርይ በጭንቅላታቸው ውስጥ በመትከል ጦርነትን ማስቀደም ዋናው ተግባራቸው ለመሆን በቃ። ከውይይትና ከሳይንሳዊ ጥናትና ክርክር ይልቅ አልገበርነትን በማስቀደምና በውጭ ኃይሎች በመመከር አገራችንን ወደ ጦር አውድማነት ለመለወጥ ቻሉ። በሌላ አነጋገር፣ ከመጀመሪያዉኑ ጭንቅላታችን በተሳሳተ ዕውቀት ስለተቀረፀ የመደማመጥ ልምድ የለንም። ሁሉሞ በየፊናው እየተነሳ ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ችግርን ከሚፈቱ ነገሮች ውጭ በመጻፍና በመለፍለፍ ሀቀኛውን መንገድ እንዳናገኝ ታግደናል። ኃይላችንና ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በስርዓት እንዳንጠቀምና ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ እንዳናስወግድ ተደርገናል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታም ለሚቀጥሉት መቶ ዓመታት ይቆያል። ይህንን እንቆቅልሽ እስካልፈታን ድረስ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እያሉ መለፍለፉ ትርጉም የለውም። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

                                                                      www.fekadubekele.com

https://www.youtube.com/watch?v=MpKwQ2i335o

 

ማሳሰቢያ፤ ስንቶቻችሁ ድረ-ገጼን እንደምትጎበኙና ድረ-ገጹ ላይም የሰፈሩትን አያሌ የፍልስፍና፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚክስ ጽሁፍች እንደምታነቡ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከሚዲያ ስርም የራሴን ብዙ ቪዲዮኖችና የቃለ-መጠይቅ ምልልሶች አስፍሬአለሁ። ድረ-ገጼን በሚመለከት እስካሁን ድረስ አስተያየት የሰጠኝ የለም። አስተያየቱ ትችትም ሊሆን ይችላል። መሻሻል ካለበትም ሊሻሻል ይችላል። ለማንኛውም ይህን የመሰለ ሳይንሳዊ ጽሁፍ ለመጻፍ ብዙ ዝግጅት፣ ማውጣትና ማውረድ ያስፈልጋል። ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም። ትምህርታዊ ለማድረግና አንባቢውም እንዲገባው ከትምህርት ወይም ከዕውቀት አኳያ መጻፍ አለበት። እንደነዚህ ያሉ ጽሁፎችን ለመጻፍ ብዙ መጻህፍቶችን ማንበብ ያስፈልጋል። ልምድንም ማካበት ተገቢ ነው። ካለበለዚያ ዝም ተብሎ አይጻፍም። ይህም ማለት ሌላውን ለማስተማርና ለአገርም ለመታገልና ትክክለኛውን የዕድገት ፈለግ ለማሳየት የግዴታ የራስን ጊዜና ኑሮ መሰዋት ያስፈልጋል። ካለበለዚያ የምንፈልገው ግብ ላይ ለመድረስ አንችልም። በጥልቅ ጥናትና ሳይንሳዊ መንገድ እያነበብን ካልጻፍንና ካልታገልን አገራችንን የግዴታ የጦርነትና የመባለጊያ መድረክ ነው የምናደርጋት። በጥብቅም እንደምንከታተለው ከሆነ ያለውም የአገራችን ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። ወደፊት በተከታታይ በሳይንስና በትክክለኛ ዕውቀት ላይ የተመሰረተና ለአገራችንም ዕድገት አስፈላጊ ጽሁፎች ለመጻፍና ለማስነበብ የግዴታ ይህን የመሰለ ድረ-ገጽና ጽሁፍ መደገፍ አለበት። ካለበለዚያ ስለትግልና ስለነፃነት ማውራት አይቻልም። ለማንኛው አስፈላጊውን ኢንፎርሜሽን ድረ-ገጼ ላይ ማግኘት ይቻላል። በተረፈ አመሰግናለሁ!!